ለቅርስ ጥበቃ የመጨረሻው አማራጭ ጥገና ወይስ እንክብካቤ?

07 Dec 2017

   

ኢትዮጵያ የህዝቧን ባህል፣ ኃይማኖት እና አኗኗር የሚያሳዩ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ነች፡፡ በርካታ ቅርሶቿንም በዓለም አቀፍ ቅርስነት ማስመዝገብ ችላለች፡፡ እነዚህን ቅርሶች በመጠበቅና በመንከባከብ ለትውልድ እንዲተላ ለፉና ኢኮኖሚያዊ ገቢ እንዲያስገኙ ጥቅም ላይ ማዋል ዋነኛው የቱሪዝም ዓላማ ነው፡፡

ይሁንና በርከት ያሉ የኢትዮጵያ ቅርሶች ከአደጋ ውጪ ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ቅርሶቹ በዕድሜም መጫን ይሁን ተገቢውን እድሳት ባለማግኘት በውል ባይታወቅም በየጊዜው አንድ በአንድ ለአደጋ እየተጋለጡ ይገኛሉ፡፡ የቅርስ ጥበቃ ሥራውም ቅርሶቹ ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስባቸው ነው የሚከናወነው የሚል ቅሬታ እየተነሳባቸው ይገኛል። የብራና መጻህፍት የመዘረፍና የመውደም አደጋ፣ የብርቅዬ እንስሳት አለመጠበቅ፣ የአክሱምና ላሊበላ የመፍረስ አደጋ መጋረጥ በስጋትነት ይነሳል፡፡

«የኢትዮጵያን ቅርሶች ለመንከባከብና ለመጠበቅ የተቋቋመ ባለስልጣን እያለ ቅርሶቹ ለምን ለአደጋ ይጋለጣሉ? በኢትዮጵያ ቅርሶች ላይ የሚሰሩ ተቋማት የቅርሶች ደህንነት አሳሳቢነት ከህብረተሰቡ ጎልቶና ቀድሞ የማይታየው ለምንድን ነው? ቅርሶችን ከጉዳት የመጠበቅ ሥራ ለምን ቅድሚያ አልተሰጠውምሲሉ በርካታ ሰዎች ጥያቄ ያነሳሉ። አዲስ ዘመንም ይህንኑ ጥያቄ የሚመለከተውን አካል ጠይቋል።

የኢትዮጵያ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተሰጠው ኃላፊነት መካከል ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የህዝቦችን ባህል፣ ቋንቋ፣ ቅርስ እንዲሁም ስነጽሁፍ የመጠበቅና ለትውልድ ማስተላለፍ አንዱ ተግባር መሆኑን ይናገራሉ። በመሆኑም የቅርሶች መጠበቅና ቅርሶችን በሚመለከት ጉዳይ ቀዳሚ ባለቤት እንደሆነም ነው የሚያመለክቱት፡፡ ሚኒስቴሩ የህዝብን ቅርስ ለመጠበቅ የሚሰራውን ሥራ በየዘርፉ በመከፋፈል በአዋጅ ከተቀመጡ ሰባት ተቋማት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ያስረዳሉ፡፡

አቶ ገዛኸኝ፤ «የኢትዮጵያ ቅርሶች በአግባቡ እየተጠበቁ ነው ወይ» ለሚለው ጥያቄ «ቅርሶች ያሉበት ቦታዎች ተጠብቀው ለሌላ አገልግሎት እንዳይውሉ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ቅርሶቹ ባሉበት ሁኔታ በበቂ ሁኔታ እየተጠበቁ አይደለም፡፡ ለቅርሶቹ በቂ በጀትና ባለሙያ ተመድቦ በሚያስፈልጋቸው ልክ አለመጠበቃቸውም አይካድም፡፡ የቅርስ ጥበቃ ሥራ ሲፈተሽ በርካታ ክፍተቶች አሉት፡፡ ቅርሶቹን መዝግቦ እውቅና ከመስጠት ባለፈ ቅርሶቹ በሚገባቸው ደረጃ እየተጠበቁ ከስጋትና ከአደጋ ነጻ ሆነው በተገቢው መንገድ እየተያዙ አይደለም» ብለዋል፡፡

ቅርሶቹን ከመመዝገብ ባለፈ ጥበቃ እንዳይደረግላቸው የቅርስ ጥበቃ እክብካቤና ጥገና እውቀትና ልምድ ያለው ባለሙያ አለመኖር እና የበጀት እጥረት ዋና ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ለኢትዮጵያ ቅርሶች እንክብካቤ ሳይሆን ለጥገና ባለሙያ ለመፈለግ የሚማተረው ወደ ውጭ መሆኑም ሌላ ችግር መሆኑን ያመለክታሉ። ባለው አነስተኛ በጀት ቅርሶቹን ለመጠበቅና ለመጠገን የሚወጣው ወጪ ደግሞ ለውጭ ባለሙያ መክፈል ያለውን ውስን በጀት በአግባቡ ለመጠቀም ፈታኝ አድርጎታል፡፡ ካለው የቅርስ ብዛት ቅርሶቹን በአግባቡ ሊጠግን የሚችል ሀብት አለመኖር አንዱ ተጠቃሽ ችግር ሲሆን፣ ይህን ማድረጉም ዘላቂ መፍትሄ ሊያስገኝ አልቻለም፡፡

አቶ ገዛኸኝ እንደሚገልጹት፤ ቅርሶች ላይ እየተሰራ ያለው ሥራ የመዳረሻ ልማት ነው፡፡ የመዳረሻ ልማት ማለት ቅርሶቹ ባሉበት አካባቢ ሆቴል፣ መንገድና ትራንስፖርት የመሳሰሉ አቅርቦቶች በማሟላት ቅርሶችን እንዲጎበኙ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ በመዳረሻ ልማት ሥራ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸው ሥራዎች በአቅም ውስንነት ምክንያት ቅድሚያ እየተሰጣቸው አይደለም፡፡ በቅርሶች አካባቢ የመሰረተ ልማት መሟላት ጎብኚዎችን ወደ ቅርሱ የመሳቢያ መንገድ ቢሆንም ቅድሚያ ለመሰረተ ልማቱ ሥራ ወይስ ለተጎዱት ቅርሶች ጥበቃ የሚለውን መወሰን ላይ ችግር አለ፡፡ ቅርሶች ከሚያስገቡት ገቢ ለመጠቀም ባይተዋር መሆናቸው ከሚያስገቡት ገቢ የራሳቸውን ደህንነት መጠበቅ አላስቻለም፡፡ በቅርሶች መገኛ ቦታዎች ላይ ያለው ማህበረሰብ ከቅርሶቹ ተጠቃሚ መሆን አልቻለም፡፡

አቶ ቸርነት ጥላሁን በቅርስና በቱሪዝም ሥራ ውስጥ ረዥም ጊዜ አስቆጥረዋል፡፡ አሁንም በኢትዮጵያ የቱሪዝም ድርጅት የመዳረሻ ቦታዎች ልማት ዳይሬክተርነት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ በኩል በተፈለገው መጠን እንድታድግና ዝቅ ብላ እንዳትታይ የማድረግ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ቅርሶቿ ናቸው የሚሉት አቶ ቸርነት፤ ኢትዮጵያ ያላት የቅርስ ሀብት አገሪቱ ካላት የኢኮኖሚ አቅም በላይ የገዘፈ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ እንዲሁም ለቱሪዝም ሥራ የጀርባ አጥንት የሆኑትን ረዥም ጊዜ ያስቆጠሩ ቅርሶች በመሆናቸው እንደ ቀላል ሊታዩና ጥበቃና እንክብካቤ ሊጎድላቸው እንደማይገባ ነው የሚናገሩት፡፡

ሁሉም የኢትዮጵያ ቅርሶች በየጊዜው ለአደጋ መጋለጥ ምክንያት ነው የሚሉትንም ያስረዳሉ፡፡ የቅርሶቹን ደህንነት አደጋ ላይ እስኪወድቅ ድረስ መጠበቁ የቅርስ ጥበቃ ስትራቴጂ አለመኖር ነው፡፡ «ቅርስ ጥበቃ ማለት መጠገን አይደለም፡፡ የቅርስ ጥበቃ ሥራ ግብ ካልተለየ አንዱን አንስቶ አንዱን መጣል፣ አንዱን ይዞ አንዱን መተው ነው የሚሆነው፡፡ በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ሥራ ያልተጠና ነው፡፡ ቅርስ ጥበቃ እውቀትና ጥበብን የሚጠይቅ በመሆኑ የቅርሶቹን አሰራር ማጥናትና በባለቤትነት መከታተል ያስፈልጋል» በማለት ያስረዳሉ። ቅርሶች ላይ የሚሰራው ሥራ ከየት ተጀምሮ የት ያበቃል የሚለውንና ቅርሶችን የተመለከተው ሥራ ከየት ተነስቶ የት መድረስ አለበት የሚለውን የሚመልስ ቅርስ ጥበቃ ስትራቴጂ ሊኖር እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡

ቅርሶችን የመጠበቅ ሥራ ላይ ለየትኛው ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ ቅደም ተከተል ማስቀመጥ ይገባል፡፡ በአጠቃላይ የተጀመረው ሥራ ሰፊ ይሆንና ከቅድመ ጥበቃ ሥራው ይልቅ ሩጫው ለችግር ከተጋለጡ በኋላ ለማዳን መጣደፍ ይሆናል ይላሉ፡፡

አቶ ቸርነት፣ ለቅርሶቹ ጥበቃ ለማድረግ ቅርሶቹ ያሉበትን አካባቢ ማህበረሰብ ባህል፣ እውቀትና ጥበብን መጠቀም ያስፈልጋል ባይ ናቸው፡፡ ሲያስረዱም «አንድ የገጠር የሳር ቤት ቤተክርስቲያንን የውጭ አገር ባለሙያዎች እንዲጠግኑ ማድረግና የአገሬው ሰው እንዲጠግን ማድረግ ልዩነት አለው፡፡ የኢትዮጵያን ቅርስ አሰራርና የቆየበትን ዘመን፣ ምስጢር፣ የአካባቢውን ሁኔታ ስለሚያስረዳ ከማንኛውም ከውጭ ባለሙያ የአካባቢው ህዝብ እውቀት ይበልጣል» በማለት ነበር፡፡ የቅርስ ጥበቃ ስትራቴጂ ቢኖር ጠቀሜታው የአካባቢውን እውቀት መጠቀም ለማስቻል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

«በጥናትም በትምህርትም የማይገኙ የማህበረሰብ እውቀቶች አሉ» የሚሉት አቶ ቸርነት፣ «ቅርስ ጥበቃ ሥራውን መስራት ያለበት ቅርሱን የሰራውና የቅርሱ ባለቤት ቅርሶቹንም እየጠበቀ እስካሁን ያቆየው የአካባቢው ማህበረሰብ እንጂ የውጭ ድርጅት አይደለም» ይላሉ፡፡ የቅርስ ጥበቃ እውቀት የህብረተሰቡን ተሞክሮ ማካተት ካልታቻለ ምንም አይነት የውጭ አማካሪ ቢመጣና ምንም አይነት ሳይንሳዊ እውቀት ቢደረደር ቸግሩን ማቃለል እንደማያስችል ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ቅርሶች በአግባቡ እየተጠበቁ እንዳልሆነ ዋነኛ ማሳያ የሆነው ብራና መሆኑን የሚናገሩት አቶ ቸርነት፣ ብራና በህግ ከአገርም ሆነ ከሚጠበቅበት ስፍራ አይወጣ ተብሎ ሲከለከል ለትውልዱ መተላለፍ የተገባውን እውቀትንም ክህሎትን እየገደበ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ይናራሉ፡፡ ነገር ግን ያሉት የብራና ጽሁፎች እንደገና እንዲባዙና በቁጥር በርክተው እንዲገኙ ማስቻል የብራና ሀብት መመናመንን ከአደጋ መጠበቅና የብራና ጽሁፍ እውቀት እንዲሸጋገር ማድረግ ይቻል ነበር፡፡

«ቅርሶችን ለመጠበቅ እየተሰራ አይደለም ማለት አይቻልም፤ ነገር ግን አሰራሩን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ቀይ ቀበሮን ለመጠበቅ መስራትና ቀይ ቀበሮ የሚኖርበትን አካባቢ ለመጠበቅ መስራት ይለያያል፡፡ የፋሲል ግንብን መጠበቅና ጎንደር አጠቃላይ አካባቢውን መጠበቅ ልዩነት አለው፡፡ እንደዚህ አይነት ልዩነቶችን የሚያሳዩ ተከታታይ የሆነ እቅድና ሥራ የግድ ያስፈልጋል» በማለት የተቀናጀ የጥበቃ ሥራ ሰፊ የተከፋፈለ ሥራን ስለሚጠይቅ ሥራው ብዙ ሆኖ የተሰራውን ያሳንሳል እንጂ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እየተሰራ ነው ቢባልም የሚሰራው ሥራ ከቅርሶቹ ዋጋ ግዝፈት አንጻር ሲታይ ግን ‹አባይን በጭልፋ› እንደሆነና የቅርስ ጥበቃ ሥራው ቋሚ ስርዓት ቢዘረጋለት አሁን በቅርሶች ላይ እየተጋረጡ ያሉትን ችግሮች ሊፈታ እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡

«በኢትዮጵያ ቅርስ አጠባበቅ ላይ ገንዘብ ችግር የሚሆን አይመስለኝም። ቅርሶቹ የሚያመጡትን ገቢ ያህል እየተጠቀሙ ነው? ቅርሶቹ እያስገኙ ያሉት የሚገባቸውን ያህል ነው ወይ? የሚለውን የሚመልስ አሰራር የለም፡፡ ቅርሶቹ ያላቸው ዋጋ ከአገሪቱ ኢኮኖሚም የገዘፈ ቢሆንም በየጊዜው ቅድሚያ ተሰጥቶ ችግሮቹ ሊቃለሉና ሊስተካከሉ አልቻሉም፡፡ የአንድ የብራና መጽሐፍ መጥፋት፣ መሰረቅና መውደም ነገ በሌላው ቅርስ ላይም እንዳይደገም ግንዛቤ መጨበጡ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ ለአደጋ እስኪጋለጡ እየተጠበቀ ነው» ይላሉ፡፡

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ዘለቀ፣ ባለሥልጣኑ በዋናነት የተሰጠው ኃላፊነት የአገሪቱን ቅርሶች አጥንቶ በመጠበቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲያስገኙና ለትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ቅርሶች በዓይነትም በቁጥርም በርካታና ተፈጥሯቸውም ውስብስብ በመሆኑ በቂ ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እንዲሁም ባለስልጣኑ ቅርሶች መጠበቃቸውን መቆጣጠር፣ እንክብካቤና ጥገና የሚያስፈልጋቸውን እንዲያገኙ ቅርሶቹን በባለቤትነት ለሚጠበቁ የግለሰብ፣ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ቅርሶቹ መጠበቃቸውን እንደሚረጋገጥ ይገልጻሉ፡፡

የሚመደበው በጀት አብዛኛው ጊዜ በዓለም አቀፍ ለተመዘገቡት ቅርሶች መሆኑ ለሌሎቹ ቅርሶች ተገቢውን ጥበቃ ላለማድረግ ጋሬጣ ሆኗል ማለት ያስደፍራል። በዚህ ዓይነት መልኩ አንዳንድ አካባቢ ያሉ ቅርሶች አደጋ ላይ ሲሆኑ፣ የሚመደብ ተጨማሪ የድጎማ በጀት እንዳለ ይጠቁማሉ፡፡ የድጎማ በጀቱም ቢሆን አነስተኛ እንደሆነ ግን አልሸሸጉም፡፡

በኢትዮጵያ ቅርሶች ጥበቃ ሲባል ሁሌም ቅርስ ጥገና መሆኑ እንደሚታሰብ የሚናገሩት አቶ ኃይሉ፣ የቅርስ ጥገና የቅርስ ጥበቃ የመጨረሻ አማራጭ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ «የቅርስ ጥበቃ ሥራ በዋናነት የዘላቂ የጥበቃና የእንክብካቤ ሥራ ነው፡፡ ዘላቂ የቅርሶችን ህልውና ማስጠበቅ የሚችል የጥበቃና እንክብካቤ ያካተተ ሥራ ነው፡፡ ዘላቂ የቅርስ ጥበቃ ሥራ ቅርሶች ባሉበት ሁኔታ እንዳሉ የመጠበቅና የመንባከብ ሥራ ነው፡፡ አብዛኛው ቅርሶች እያረጁ ዘመናትን የሚሻገሩ በመሆናቸው ቅርሶቹ ባሉበት ሁኔታ ተጠብቀው እንዲቆዩ ማድረግ ነው» ይላሉ፡፡

አቶ ኃይሉ፣ «የኢትዮጵያ ቅርሶች ጥበቃ አይደረግላቸውም» በሚለው አይስማሙም፡፡ «ቅርሶች በአግባቡ እየተጠበቁ ነው» ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ቅርሶቹ እስካሁን ድረስ ለትውልድ መተላለፋቸው ስለተጠበቁና እስካሁን መቆየታ ቸውም ባሉበት አካባቢ ማህበረሰብ በባህልና በታሪክ መጠበቃቸውን ማሳያ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን ቅርሶችን እውቅና ከመስጠት ባለፈ በአግባቡ የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራው በአግባቡ እየተሰራ ነው ለማለት እንደማያስደፍር አልሸሸጉም፡፡

የኢትዮጵያ ቅርሶች አጠባበቅ ላይ ያለው ዋናው ክፍተት የቅርስ አስተዳደር አለመኖር ነው በማለት የቅርስ ጥበቃ ሥራው ቅርሱን በትክክል ከማስተዳደር ጋር እንደሚያያዝ ያስረዳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቅርሶች አለመጠበቅ ዋነኛ ችግር እያንዳንዱ ቅርስ የራሱ አስተዳደር አለመኖሩ ከአካባቢው ማህበረሰብ ባለፈ ቅርሶቹን በባለቤትነት የሚያስተዳድር አካል ባለመኖሩ የሚሰራው የቅርስ ጥበቃ ትርጉም እንዳይኖረው ማድረጉ ነው፡፡ ስለዚህ የቅርሶችን የየዕለት ሁኔታ በመደበኛነት የሚከታተል የቅርስ አስተዳደር ስርዓት ሊኖር ይገባል፡፡ ነገር ግን የቅርሶችን ሁኔታ በኃላፊነት በየዕለቱ የሚከታተልና የሚጠብቅ የለም፡፡ ቅርሶች በየጊዜው በሚደረግ ክትትል እንክብካቤና ጥበቃ ባለመኖሩ አብዛኛውን ጊዜ የመጨረሻ አማራጭ የሆነው ጥገና ላይ እንዲደርሱ አድርጓል፡፡ ቅርሶችን አስቀድሞ ከጉዳት መጠበቅና መንከባከብ ስለሚቻል እድሳት እንደማይመከርም ይናገራሉ፡፡ ጥገና ደረጃ ላይ ከደረሰም የቅርሱን ይዘት ሊለውጥ የማይችል መሆን እንዳለበት ያመለክታሉ፡፡ የቅሶቹን ሁኔታ በየቀኑ የሚከታተል ባለመኖሩ ቅርሶቹ አደጋ ላይ ሲደርሱ የሁሉም ትኩረት አንድ ጊዜ ብራና፣ አንድ ጊዜ ጣና፣ አሁን ደግሞ ላሊበላ ላይ እንዲሆን አድርጓል በማለትም ያስረዳሉ፡፡

የቅርሶቹን ሁኔታ የሚመለከት የክልሎች የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች በቅርብ ጊዜ ቢቋቋሙም ሁሉም ጽህፈት ቤቶች ከመቋቋም ባለፈ የቅርስ ጥበቃ ክፍልና ሥራ ያልተጠናከረበትና ባለሙያ የሌለው መሆን፣ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ በዩኒቨርሲቲዎች በትምህርት ደረጃ የሚሰጡት በመቀሌና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ መሆኑና ተምረው የጨረሱት ባለሙያዎች በጣት የሚቆጠሩ መሆን የቅርስ ጥበቃ ሥራው ችግር ነው፡፡ ቅርሶቹ በዕድሜ ብዙ ዘመን ያስቆጠሩ በመሆናቸው በየዕለቱ የሚያስፈል ጋቸውን ክትትል ባለማግኘታቸው ነው ለአደጋ እየተጋለጡ ያሉት፡፡

ሁሉንም የቅርስ ጥበቃ ሥራ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለረዥም ዓመት ከዋና መስሪያ ቤት ባለሙያዎችን በመላክ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ አሰራር ግን ለቅርሶቹም ደህንነት ለአሰራርም አዋጭ እንዳልሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ማንኛውም ቅርስ ለአደጋ ከተጋለጠ ትኩረት ስለሚሰጠው አሰራሩን ቅርሶች ለአደጋ ሲጋለጡ ማተኮር እንዲሆን ማድረጉ ነው፡፡ ይህ አሰራር ደግሞ በዓለም አቀፍ የቅርስ አጠባበቅ ስምምነት የማይተገበር ነው፡፡ ከስምምነቱ አንዱ መስፈርት የሆነው ቅርሶች ሲመዘገቡና ከተመመዘገቡ በኋላ የሚተዳደሩበት ስርዓት እንዲኖር የሚጠይቅ ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ቅርሶች ለዓለም አቀፍ ቅርስነት ሲመዘገቡ እስካሁንም የራሳቸው የቅርስ አስተዳደር ስርዓት የላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ቅርሶች የቅርስ አስተዳደር ስርዓት እንደሚያስፈ ልጋቸውና ወደ አሰራሩ መግባት ግዴታ ሆኗል፡፡ የአስተዳደር ሥራው የቅርሶችን ይዞታና ሁኔታ በየዕለቱ መከታተል የሚያስችል ነው፡፡ ቅርሶቹ በየወቅቱ ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና ምን ቅድሚያ ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት የሥራ ቅደም ተከተል ማስቀመጥ የሚያስችል ነው፡፡ ቅርሶች አደጋ ላይ ሲደርሱ ብቻ ከመረባረብ ያሉበትን ደረጃ በየጊዜው በመከታተል እንክብካቤ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡

በቅርስ ጥበቃ በኩል በቀጣይ ሊሰራበት የሚገባው የጥበቃና የእንክብካቤ ሥራ መሆኑን አቶ ኃይሉ ይስማማሉ፡፡ የቅርሶቹን የየዕለት ሁኔታ የሚከታተል ባለሙያ ቢኖር አሁን ያለውን የቅርስ ጥበቃ ሥራ በማሻሻል ከአደጋ ጊዜ ርብርብ ወደ እንክብካቤ ትኩረት መለወጥ ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ቅርሶች ላይ በየጊዜው የሚጋረጠውን አደጋ በመቀነስ ቅርሶች አደጋ ውስጥ ሲሆኑ የሚሰራው የጥድፊያ ሥራን ያስቀራል፡፡

የኢትዮጵያ ቅርሶች አሰራር ከዓለም የቅርስ ጥበቃ እውቀት የተለዩና የተወሳሰቡ መሆናቸው በጥገና ጊዜ የሚያጋጥም ፈተና እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ኃይሉ፣ ለአብነትም «የኢትዮጵያ ቅርሶች አሰራር ውስብስብነትን ሊያሳይ የሚችለው አንዱ ላሊበላ ነው፡፡ በቅርሱ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመጠገን በቂ እውቀት ያለው ባለሙያ በአገር የማግኘቱ ጉዳይ አሳሳቢ ነው ይላሉ። ከውጭ ደግሞ በቴክኖሎጂም ጭምር አልተገኘም፡፡ ላሊበላ መጠገን እያለበት መጠለያ ብቻ እንዲሰራለት ያስገደደው የጥገና እውቀቱ ባለመገኘቱ ነው፡፡ እውቀትና ክህሎት አለን የሚሉ በርካታ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች መጥተዋል፡፡ ነገር ግን ከላሊበላ ተፈጥሮ ጋር ሲስተዋል ሥራቸው መፍትሄ ለመሆን አይችልም» ብለዋል፡፡

«የቅርስ ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ውስጥ እስከ 50 የሚደርስ ባለሙያ ሊኖር ቢገባም ነገር ግን ያሉት ባለሙያዎች ከ20 የሚያንሱ ናቸው» በማለት የባለሙያ እጥረት ተጨማሪ የዘርፉ ፈተና መሆኑን ይናራሉ፡፡ ባለሙያ አልተገኘም ሲባል ሙሉ ለሙሉ ባለሙያ የለም ማለት ሳይሆን የቅርስ ጥበቃ ክህሎት ልምድ ያለው ባለሙያ እጥረት ለማለት ነው፡፡ እንዲሁም የቅርስ ጥገና ባለሙያ መሰረቱ ምህንድስና፣ አርኪኦሎጂ የመሳሰሉ ተያያዥ ዘርፎችን የሚጠይቅ በመሆኑ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ባለሙያዎችን ከሌሎች የሥራ ዘርፎች ጋር ነው እየተሻማን ያለነው፡፡ በተጨማሪም ባለስልጣኑ የሚጠይቀው ማሟያ ከፍተኛ መሆኑና ሌሎች ተቋማት የሚያቀርቡት ክፍያ ከፍተኛ በመሆኑ የቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች እንዳይበረክቱና ከቅርስ ጥበቃ ይልቅ በሌላ ዘርፍ እንዲሰማሩ አስገድዷል፡፡

«ከቅርስ ጥበቃ ሥራ ይልቅ የጥገና ሥራ ከፍተኛ ወጪ አለው፡፡ የቅርስ ጥበቃ ሥራ ጥገና ላይ ከደረሰ ለቅርሱም አይመከርም፤ ወጪውም ከፍተኛ ነው፡፡ በባለሥልጣኑ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሚመደበው በጣም አነስተኛ በጀት ነው፡፡ በጀቱ አብዛኛው የሚውለው ለእንክብካቤ አይደለም፡፡ ካሉት የቅርሶች ብዛትና ውስብስብነት አንጻር ሚመደበው በጀት በጣም አነስተኛ ነው» በማለት ያብራራሉ። የቅርስ ጥበቃ ሥራ ዋነኛ ችግሮች መካከል በጀት አንዱና ዋነኛው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለቅርስ ጥበቃ የተመደበው በጀት 30 ሚሊዮን እንደሆነና ይህንን ገንዘብ ለእያንዳንዱ ቅርስ ሲከፋፈል ትልቁ ድርሻ 2ሚሊዮን እንደማይደርስ ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ደግሞ ጥገናው ቀርቶ አነስተኛ የጥበቃ ሥራዎችን ለመስራት እንኳን በቂ አይደለም፡፡

አቶ ኃይሉ፣ ቅርሶቹ በያሉበት አካባቢ የአስተዳደርና የእንክብካቤ ሥራን ለመጀመር የባለሙያ ቅጥር ለማካሄድ ማስታወቂያ ቢወጣም ሁለት ጊዜ ሳይሳካ መቅረቱን ይናገራሉ፡፡ ለባለሙያዎቹ የተቀመጠው መስፈርት የዓለም አቀፍ የቅርስ ጥበቃ ደረጃ ያለው ቢሆንም መስፈርቱን ሊያሟላ የሚችል ባለሙያ አልተገኘም፡፡ አሁን በድጋሜ ለሶስተኛ ጊዜ ማስታወቂያ ማውጣቱንና በቀጣይ የቅርስ ጥበቃ ሥራውን ከቅርስ አስተዳደር ለመጀመር እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡት የዘርፉ ባለሙያዎች አሁን ያለው አሰራር ቅርሶቹን በሚገባ ለመጠበቅና ለመንከባከብ ባለማስቻሉና ለቅርስ ጥበቃ ሥራው መሻሻልና ቅርሶች ላይ ከተጋረጠው እንክብካቤ እጦት ይታደጋል ያሉትን ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ከበጀት በተጨማሪ ቅርሶቹ ከሚያስገቡት ገቢ ለእንክብካቤያቸው መመደብ ይገባል፡፡ የአካባቢው ህብረተሰብ ቅርሱን የራሴ ነው ብሎ እየጠበቀ ቢሆንም ከቅርሶቹ ጥቅም የሚያገኝበት መንገድ ማበጀት እና የቅርስ አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡

 

ሰላማዊት ንጉሴ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።