ሰባ ዓመት በስኬት Featured

11 Jan 2018

ከዕድሜ ባሻገር በሥራ ቢመዘን ‹‹አንጋፋ›› የሚለው ቃል በሚገባ ይገልፀዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ሰባኛ ዓመት የልደት ሻማውን ሲያበራ በሦስት የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ ስኬትን ጠብቆ የአገር ምልክት መሆኑን አስመስክሯል፡፡ ከአገር አልፎ የጥቁር ህዝቦች ኩራት ሆኖ የዘለቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬም አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ማስተሳሰሩን ቀጥሏል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ለአካባቢ ጥበቃ የተቆርቋሪነት መርህ አንግቦ የተቋሙን አሰራር ወረቀት አልባ የማድረግ ጥረቱን በብዙ መንገድ ማሳካቱን ተያይዞታል፡፡ ይሄም ከቢሮ ውስጥ ሥራ እስከ ደንበኞች የትኬት አቆራረጥ ድረስ የተሳሰረ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡
አየር መንገዱ የዚህ ጥረቱ አካል የሆነውን አዲስ አገልግሎት በቅርቡ አስተዋውቋል፡፡ በሞባይል አፕሊኬሽን የተቋሙ ደንበኞች ከቅርንጫፍ ቅርንጫፍ መጓጓዝ ሳይጠበቅባቸው ባሉበት ስፍራ ሆነው ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ነው፡፡ ሰሞኑን በተደረገ መርሐ ግብር ላይ ቴክኖሎጂውን ያስተዋወቁት የአየር መንገዱ የአይቲ ክፍል ባለሙያዎች በስራቸው ከፍተኛ ምስጋና ተችሯቸዋል፡፡ የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም አፕሊኬሽኑን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፤ ደንበኞች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አየር መንገድ የተቋሙን አሰራር ይበልጥ በቴክኖሎጂ ለማዘመን ጥረት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡
አየር መንገዱ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ሦስት መንግሥታት ፖሊሲ ውስጥ ቢያልፍም ከስኬት ወደኋላ የጎተተው አጋጣሚ እንብዛም አልነበረም፡፡ ከሰባ ዓመት በላይ በአህጉሩ የአየር መንገዶች ታሪክ የስኬት ጉዞ ለመዝለቁ የመላው ሠራተኛ ትጋት ውጤት መሆኑን የገለጹት አቶ ተወልደ፤ ተቋሙ አሁንም ብዙ ውድድር በበዛበት ዘርፍ ትርፋማነቱን እንዳስጠበቀ ለመዝለቅ ያስቻለው ይሄው ትጋቱ ነው፡፡ ከተቋሙ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ያለፈው ዓመት እ.አ.አ 2017 ለአየር መንገዱ ታሪካዊ የስኬት ዘመን በመሆን አልፏል፡፡ የበረራ መዳረሻ መስመሮች ከማበራከት ባሻገር ተቋሙ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ የተረጋጋ ጉዞ ላይ መገኘት ማለት ይሄ ነው፡፡
ሥራ አስፈፃሚው አቶ ተወልደ ‹‹ባለፉት ሰባት ዓመታት አየር መንገዱ ባስቀመጠው ስትራቴጂያዊ ፍኖተ ካርታ አማካኝነት በጣም ተለዋዋጭ፣ የማይጨበጥ፣ ውስብስብና አሻሚ በሆነው ዘርፍ ውስጥ ዘላቂነት ያለው ፈጣንና ትርፋማ ጉዞን ማድረግ ችለናል›› በማለት፤ ተቋሙ ባስቀመጠው ራዕይ 2025 መሰረት እ.አ.አ 2017 ብቻ 12 አዳዲስ መዳረሻዎች በረራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ዘመናዊና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀሙ ማጓጓዣና ዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች በመጠቀም አገልግሎቱን በማሳደግ ላይ ይገኛል፡፡ በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመትም ይሄንኑ ጅምር በማጠናከር በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱ እንደሚቀጥል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ይገልጻሉ፡፡
የአየር መንገዱን ትርፋማነት በተመለከተ አምና ከአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ ተለዋዋጭነት ጋር በተያያዘ የዘንድሮውን ግማሽ ዓመት ትርፍ መገመት ባይቻልም ባለፈው ዓመት ግን 260 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ መገኘቱ ተጠቅሷል፡፡ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያን በተመለከተም፤ ለተጓዦች የጉዞ አገልግሎት ከመስጠት በተጓዳኝ በአውሮፕላን ጥገና ያለውን ልምድ ይበልጥ ለማሳደግ ከተለያዩ ጥገናዎች በተጨማሪ የሦስት ትላልቅ ጋራጆች ግንባታ አከናውኗል፡፡ በዕቃ መጫኛ አገልግሎቱም በግዝፈቱ ከአፍሪካ የቀዳሚነት ደረጃ የሚያሰጠውና ከአምስተርዳሙ ስቺምፖል እንዲሁም ከሲንጋፖርና ሆንግ ኮንግ ጋር ተወዳዳሪ የሆነ ነው፡፡
በሌላ በኩል በተያዘው ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚጀምር የሚጠበቀው ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል የአየር መንገዱን አገልግሎት በከፍተኛ ሁኔታ የሚሳድገው ይሆናል፡፡ በከተማዋ ተጨማሪ ግዙፍ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከመያዙም ባሻገር በአህጉሩ የመጀመሪያው የሆነ ትልቅ የቻይናውያን ሬስቶራንትም እንደሚኖረውም ታውቋል፡፡ በማሰልጠኛም ዘርፍ የተሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ጉዞውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
አየር መንገዱ ባስተዋወቀው የሞባይል አፕሊኬሽን የቲኬትና ተጓዳኝ አገልግሎቶች ማስተዋወቂያ ላይ የአየር መንገዱ የረጅም ጊዜ ደንበኞችና የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች ታድመዋል፡፡ እንዲህ ያለው መድረክ በተለይም በስኬቱ ተጠቃሽ በሆነ ተቋም በኩል ሲደገስ ለልምድ ልውውጥ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡ በመድረኩ የታደሙ አካላትም ይሄን የሚያንፀባርቁ ሃሳቦች አንሸራሽረዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የአየር መንገድ ውድድሩ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከመጠየቅ አንስቶ በዘርፉ እስከሚስተዋሉ አንኳር ማነቆዎች ላይ እስከመወያየት የደረሰ የሃሳብ ማንሸራሸሪያ አጋጣሚን ፈጥሮ ነበር፡፡
ስኬትን በተመለከተ ከሰባ ዓመቱ ታሪክ ይልቅ ያለፈውን ሰባት ዓመት ሁኔታ በማስቀደም ንግግራቸውን የሚጀምሩት ዋና ስራ አስፈጻሚው ‹‹ያለፉት ሰባት ዓመታት በአፍሪካ አየር መንገዶች ታሪክ በጣም ፈተና የበዛባቸው ዓመታት ነበሩ›› ይላሉ፡፡ በተለይም የኢቦላ ወረርሽኝ፣ እየተስፋፋ የመጣው የሽብርተኞች እንቅስቃሴ፣ የእርስ በእርስ ጦርነት፣ በአንዳንድ አገሮች የተስተዋለው የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲሁም ሌሎች ምጣኔ ሀብታዊ ማሻሻያዎች አጠቃላይ ዘርፉን በፈተና አንቀው የያዙት ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ጫናዎች ያስከተሏቸውን ቀውሶች በመቋቋም በዕድገት ጉዞ የቀጠለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ አዳዲስ መዳረሻዎችን በአዳዲስ መጓጓዣዎች ሲያደርግ ነበር፡፡
ታዲያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች በተለየ ለምን በስኬት ዘለቀ? ይሄን ጥያቄ ያነሱት የፌር ፋክስ አፍሪካ ፈንድ ሊቀመንበር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፤ ለመሆኑ ተቋሙ ከሰባ ዓመት በላይ ከዘለቀው ስኬቱ ባሻገር ያለው ሚስጥር ምን ይሆን? ሲሉ ጥያቄያቸውን ያጠናክራሉ፡፡ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ፤ በስኬት ለመዝለቁ በርካታ ሚስጥሮች መኖራቸውን ያብራራሉ፡፡ እነዚህ ሚስጥሮች ከተቋሙ የላይኛው አስተዳደር ጀምሮ መላውን የአየር መንገዱ ሰራተኞች ዋጋ የሚያሰጥ መሆኑን በማብራራት፡ አንድ ተቋም ‹‹መሪውን ይመስላል›› እንዲሉ የመጀመሪያው የስኬት ሚስጥር አመራሩ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የተቋሙ ሠራተኞች በሙሉ ከታችኛው እስከ ከፍተኛው አመራር ድረስ ያካበቱት ሰፊ ልምድና በውስጣቸው ያለው ቁርጠኝነትን በጉልህ የሚጠቅሱት አቶ ተወልደ፤ ይሄ ልምድና ቁርጠኝነት ተቋሙ ያለፈባቸውን ፈተናዎች በጥንካሬ እንዲሻገር ምክንያት መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች ደመወዝ ከሌሎች አገራት የአየር መንገድ ሠራተኞች ደመወዝ ጋር የሚነፃፀር አይደለም›› የሚሉት አቶ ተወልደ፤ ሰራተኞች ከገንዘብ ይልቅ ለብሔራዊ ተልዕኮ ቁርጠኛ ሆነው መስራታቸው የስኬት ሌላኛው ሚስጥር ያደርጉታል፡፡
‹‹አየር መንገዱ ሕይወታችን ነው›› ሲሉ የአየር መንገዱን ሠራተኞች በመወከል የገለጹት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ ከ13ሺ በላይ የሆነው የአየር መንገዱ ሠራተኛ ያለውን ብቃት በሙሉ ለቆመለት ዓላማና ተልዕኮ በሕብረት መጓዙ ለስኬት እንዳበቃው ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ተቋሙ የሚመራበት አስተዳደር ለሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ምሣሌ ያደርገዋል ይላሉ፡፡ ለአብነትም የአየር መንገዱ ባለቤት መንግሥት ቢሆንም የአየር መንገዱ የዕለት ተዕለት ሥራ የሚከናወነው ግን በባለሙያዎች ብቻ ነው፡፡ ‹‹በአየር መንገድ ቢዝነስ ይሄ ተሞክሮ በጣም ጥቂት በሚባሉት ዘንድ የሚተገበር ነው›› የሚሉት አቶ ተወልደ፤ ተሞክሮውን በአግባቡ ለተጠቀመበት በግል ኢንቨስትመንትም ውስጥ ባለቤትነትን ከአስተዳደር ነጥሎ መመልከት ለስኬት ያበቃል፡፡ ምክንያቱም በዓላማና ድርሻ መካከል ያለውን ልዩነት በአግባቡ መረዳት ጠቃሚ ጉዳይ ይሆናል፡፡
እንደ አህጉር በአፍሪካ የተለያዩ አገራት የመንግሥት አየር መንገዶች በአስተዳደራቸው ውስብስብ ችግር ምክንያት ብዙ ፈተና እንደገጠማቸው ያስታውሳሉ፡፡ አስራ አንድ አባል አገሮችን የሚያቅፈው ኤር አፍሪክ ጨምሮ የናይጄሪያ፣ የጋና፣ የዛምቢያ እንዲሁም የዚምባብዌ አየር መንገዶች ዛሬ ታሪክ ሆነው ለመቅረታቸው ምክንያቱም በመንግሥትና በተቋም አስተዳዳሪዎች መካከል ያለው የሚና ልዩነት በአግባቡ ባለመፈተሽ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህ አየር መንገዶች በነበረባቸው የበዛ ጣልቃ ገብነት ምክንያት አስተዳደራቸውም እየተሽመደመደ ሊሄድ ችሏል፡፡
በአጠቃላይ አየር መንገዱ በርካታ ተጓዦችን ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ ሲያጓጉዝ አብራ የምትጓዘው አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያን በመላው ዓለም በአምባሳደርነት የሚያስተዋውቀው አየር መንገዱ፤ በጥቁር የነፃነት ትግል ውስጥ ለበርካታ ፋኖዎች የብርታት ስንቅ ሆኖላቸዋል፡፡ ይሄ የአየር መንገዱ አለም አቀፋዊ ዝና በአገሪቱ ለሚገኙ በተለይም የአፈፃፀም ችግር ላለባቸው ተቋማት ምሳሌ ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይም በሚሰጧቸው አገልግሎቶች በየጊዜው ሕዝብን የሚያማርሩ ተቋማት ጎራ ብለው ልምድ መቅሰም ይገባቸዋል፡፡ አየር መንገዱም ልምዱን ለማካፈል በሩን ይበልጥ መክፈት ይጠበቅበታል፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።