አሳሳቢው የጀነቲክ ሀብት ዝውውር

13 Jan 2018

በአገሪቱ የጀነቲክ ሀብት ዝውውርን በተመለከተ አዋጆች ወጥተው መተግበር ከጀመሩ በርካታ ዓመታትን አስቆጥረዋል። የአዋጆቹን ተግባራዊ መሆን እንዲከታተል ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ቢሆንም፤ አጋዥ አካላትም ከጎኑ ሆነው ለተግባሩ የበኩላቸውን እያበረከቱ ይገኛል፡፡ ሆኖም የእነዚህ ባለድርሻዎች ተሳትፎና ድጋፍ በሚፈለገው ልክ አይደለም፡፡ በዚህም ያለ ኢንስቲትዩቱ ፈቃድ ማንኛውም የጀነቲክ ሀብት ዝውውር እንዲደረግ ባይፈቀድም፤ በተወሰነ መልኩ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት ሌሎች ተቋማት ግን ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠታቸው ዝውውሩ እየተፈፀመ ነው።
ይህ የጀነቲክስ ዝውውር ደግሞ በአገር ውስጥ ያለውን ወደውጭ በማውጣት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፤ ከውጭም በሚገቡት ላይም ክፍተት እንዲፈጠርና አገሪቱ በተለያየ አጋጣሚዎች ችግር ውስጥ እንድትገባ እያደረጋት መሆኑን ሰሞኑን በቢሸፍቱ ከተማ በተደረገና በዘርፉ ሥራ ላይ ባተኮረ የባለድርሻዎች የጋራ ውይይት ላይ ተነግሯል። በወቅቱ እንደተነገረው፤ የጀነቲክ ዝውውር ቁጥጥሩ በአብዛኛው የሚሸፈነው በኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ቢሆንም፤ በኬላዎች ላይና በጉምሩክ አካባቢ በሚታዩ የፍተሻ ክፍተቶች፣ እንዲሁም ግብርና ምርምር በሚሰሯቸው የተወሰኑ ሥራዎች ለተቋሙ ፈተና መሆናቸውን ነው፡፡
ኢንስቲትዩቱ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 291/2005 አንቀጽ 6 (19) እንዲቋቋም ሲደረግ በጀነቲክ ሀብትና አርክቦት የማህበረሰብ መብቶች አዋጅ ቁጥር 482/1998 አንቀጽ 14 ንዑስ አንቀጽ አንድ እና ደንብ ቁጥር 169/ 2001 አንቀጽ 23 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ በተሰጠው ኃላፊነት እንዲሰራ ታስቦ ነው። ነገር ግን ዛሬ ላይ ይህ ችግር በተለያየ መልኩ ሰፍቶና ከተቋሙ አቅም በላይ እየሆነ በመምጣቱ ከውጭ የሚገቡትም ሆኑ ከአገር የሚወጡት የጀነቲክ ሀብቶች እየተበራከቱ መምጣታቸው ነው የተነገረው፡፡ ይሄን ችግር መነሻ ያደረገው የጋራ መድረክም በጉዳዩ ዙሪያ የተከናወኑና ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ጥናቶች ቀርበው ውይይት የተደረገበት ነበር፡፡
አቶ አማረ ሰይፉ፣ በመድረኩ ላይ የውይይት ጽሑፍ አቅራቢ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደተናገሩት፤ የጀነቲክ ዝውውር ሲነሳ ከውጭም ሆነ ከውስጥ ባሉት ዝርያዎች ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ይዳሰሳሉ። ስለሆነም ወራሪ መጤ ዝርያዎች በሁለቱም መልኩ ሊከሰቱ ይችላሉ። ይህ ችግር ደግሞ በተለይም ከውጭ በሚገቡ ዝርያዎች ላይ የሰፋ ነው። ምክንያቱም አገር በቀል ስላልሆኑ ከተፈጥሮ መገኛ ሥርዓተ ምህዳር ውጭ በፍጥነት መስፋፋት የሚችሉና የሥርዓተ-ምህዳርን መስተጋብር በማዛባት በብዝሃ ሕይወት ሀብት ላይ፣ ኢኮኖሚና በሰው ልጅ ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ የዕፅዋት፣ የእንስሳት ወይም የደቂቅ አካላት ዝርያዎች እንዲፈጠሩ ያደርጋሉ።
እንደ አቶ አማረ ገለፃ፤ የዓለም አቀፉ ብዝሀ ሕይወት ስምምነት አባል አገራት ወራሪ መጤ ዝርያዎች ወደ ሀገር ገብተው በሥርዓተ-ምህዳርና ዝርያዎች ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ የቅድመ- መከላከል፣ መቆጣጠርና ማስወገድ ተግባራትን ማከናወን እንዳለባቸው ይገልፃል፡፡ ነገር ግን በዝውውሩ ሳቢያ ይህ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ ተቋማት የሚያከናውኗቸው ሥራዎች ቢኖሩም፤ በዋናነት የሚመለከተው የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት በመሆኑ ጀነቲክ ሀብቶችን የማወቅ፣ የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራዎችን በቁርጠኝነት ይሠራል። ይሁንና በኢንስቲትዩቱ ብቻ ያለው ተግባር የሚከናወን ስላልሆነ በርካታ ወራሪ መጤ ዝርያዎች አገር ውስጥ እንዲገቡ ዕድል በመስጠት ችግሮች እንዲንሰራፉ ማድረጉን ያስረዳሉ።
ባለው የሰው ኃይልና ለሌሎች ተቋማት የተሰጠው ኃላፊነት በአግባቡ ባለመፈጸሙ የተነሳ አገሪቱ አሁን ላይ በርካታ ችግሮች እንዲገጥማት እየሆነ መጥቷል የሚሉት አቶ አማረ፤ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ ወራሪ መጤ ዝርያዎች ከሚባሉት መካከል በሁሉም ዘንድ አስፈሪ የሆኑት መጤ ዝርያዎች እየታዩ መሆኑን ያነሳሉ። ዋና ዋናዎቹም ፈረምሲሳ ወይም ቅንጬ አረም፣ እንቦጭ አረም፣ የወፍ ቆሎ፣ አትንኩኝ፣ ሆቆንቆል፣ ነጭ ለባሽ፣ ብጫ ለባሽ፣ የዱር ትንባሆ፣ ባናዳ፣ አቀንጭራ፣ ቆሬ ሀሬ፣ ሹናሹና፣ ካልሎሮፒፒስ ሱአራ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። የጉዳትና የሥርጭት አድማሳቸውም ቢሆን እንደ ሥርዓተ-ምህዳሩ ሁኔታ ይለያያል፤ ለምሳሌ ወደ ሀገራችን በምስራቅ በኩል በምግብ እርዳታ ማጓጓዣ መርከቦች አማካኝነት በድንገት እንደገባ የሚነገርለትና በድሬዳዋ አካባቢ እየተከሰተ ያለው ፈረምሲሳ አንዱ ነው ይላሉ። ዝርያው በከፍተኛ ፍጥነት በመስፋፋትና የግጦሽና እርሻ መሬቶችን በመውረር ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለ ነው።
በተመሳሳይ ፓርቴኒየም የሚባለው ዝርያ የሚራባበት እና የሚዛመትበት መንገድ በዘሩ አማካኝነት ስለሆነና ክብደቱ ቀላል በመሆኑ በወራጅ ውኋና በነፋስ፣ በከብቶች ፀጉር፣ በተሸከርካሪ፣ ከእርሻና ከግንባታ መሳሪያዎች ጋር በመጣበቅ፣ በአሽዋ፣ ከሰብል ዘሮች ጋር በመቀላቀልና በከብቶች መኖ አማካኝነት ወደ ተለያዩ ቦታዎች ይዛመታል። ይህ ደግሞ አዳዲስ አካባቢዎችን በፍጥነትና በስፋት የሚወርበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንዳደረገም ይገልፃሉ።
ለመራባት የሚያስችል ከፍተኛ የዘር ምርት ያለው፣ በሁሉም ሥርዓተ-ምህዳሮች የሚላመድና የሚለማ፣ ድርቅ መቋቋም የሚችል፣ ሌሎች ዕፅዋቶችን የሚፃረር ኬሚካል ማመንጨቱና በአጭር ጊዜ ፈጣን እድገት ያለው መሆኑ ደግሞ ከሌሎቹ ዝርያዎች ከፍተኛ ጉዳት የማድረስ ኃይል አለው። ከብዛቱ የተነሳ የሰብልን አበባ በመሸፈን ሰብል ዘር እንዳያፈራና መካን እንዲሆን ያደርጋል። የሚያመነጨው ኬሚካል የሌሎችን ዕፅዋት የዘር ብቅለትና የሰብል ዕድገት ይገታል፣ በግጦሽ መሬት ላይ በመብቀል የግጦሽ ብዘሀ ሕይወትና ምርት እንዲቀንስ ያደርጋልም ብለዋል።
ይህ አረም፣ በዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች ሥርዓተ-ምህዳር ላይ የሥነ-ሕይወት ቅንብር ለውጥና መናጋትን ያስከትላል፣ የአንጀት፣ የኩላሊትና ጉበት በሽታዎች ያመጣል፣ እንስሳት ከተመገቡት የወተትና የሥጋ ጣዕምን ይቀይራል። የማር ምርትን ይቀንሳል፣ ጣዕሙንም ይቀይራል። ሰዎች ከአረሙ ጋር ለረዥም ጊዜ በሚነካኩበት ወቅት የሰውነት መቆጣት፣ ድካም፣ የሰውነት መቀነስ፣ የቆዳ በሽታ፣ ትኩሳት፣ አስም፣ ብሮንካይትና ሌሎች ተያያዥ የጤና ችግሮችን ያስከትልባቸዋል። እናም እነዚህ ነገሮች መወገድ የሚችሉት ሁሉም በተሰጠው ኃላፊነት መሥራት ሲችል ነውና የጀነቲክ ዝውውሩ ላይ ጥንቃቄው መጠንከር እንዳለበት አበክረው ያስገነዝባሉ።
በኢንስቲትዩቱ የህግ አማካሪ አቶ ፍቅረማርያም ግዮን በበኩላቸው፤ ተቋሙ የተለያዩ ተግባራትን በኃላፊነት እንዲሰራ ተሰጥቶታል። ይሁንና የበጀትም ሆነ የሰው ኃይሉ ይህንን ያህል ሥራ ለመሸከም የሚያስችለው አይደለም። ነገር ግን ካለው ፍላጎትና ቁርጠኝነት አንፃር ዓለማቀፍ ስምምነቶችን እያደረገ የጀነቲክ ዝውውር ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ ይሰራል። በዚህ ደግሞ በየጊዜው ለውጦች እየታዩ መሆኑን ይናገራሉ።
ኢንስቲትዩቱ ጠንካራ የሆኑ አሰራሮችና መመሪያዎች እንዲሁም ከመንግሥት የተሰጡት ጥብቅ ፖሊሲዎች እንዳሉት እና በዚህም ከመቅጣት ይልቅ ማስተማርን አስቀድሞ እየሰራ እንደሚገኝ፤ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን ሀብት በማፈላለግ እንደሚተገብርም ይናገራሉ። ሆኖም ከተቋማት ጋር በጥምረት የመሥራቱ ሁኔታ የላላ በመሆኑ ክፍተቶቹ ሊሰፉ ችለዋልና የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት እንዳይቻል እንቅፋት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ በተለይም ፕሮሶፒስ የተባለው ወራሪ መጤ ዝርያ በቆላማ አካባቢዎች በመራባቱና በመሰራጨቱ በአርብቶ አደሮችና በከፊል አርብቶ አደሮች ላይ እያሳደረ ያለው የኢኮኖሚ ጫና ቀላል እንዳልሆነ ይገልፃሉ።
ወራሪ መጤ ዝርያዎች አገሪቱ በምትፈልገው ደረጃ እንዳታድግና ህዝቡም የምግብ ዋስትናውን እንዳያረጋግጥ እንቅፋት መሆናቸው በየአካባቢው የሚታይ ጉዳይ ነው። ስለሆነም ለብዝሀ ሕይወት መመናመንና መጥፋት አንዱና ዋነኛው ምክያቱ ተቋማት በተሰጣቸው ልክና ለአገር በሚጠቅም መልኩ አለመሥራታቸው እንዲሁም ትኩረት ለብዝሀ ህይወት ጥበቃ ያለመስጠታቸው ነውና የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት ብቻ ሳይሆን ሁሉም የድርሻውን ያድርግ ይላሉ።
የውይይቱ ተሳታፊ ዶክተር ሀብቴ ጃቢሳ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የጀነቲክ ዝውውር ጉዳይ ከአገር ውስጥ የሚወጡትንም መጠበቅ ላይ ያተኩራል። ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ ቁጥጥሩ በባለሙያዎችም ሆነ በኃላፊዎች ዘንድ እንዲሁም በሠራተኛው ላይ የላላ ይመስላል። ምክንያቱም ይህ ሀብት የእያንዳንዱ ዜጋ መሆኑን መገንዘብ ላይ ስለሚቀር ነው። በተለይም ትልልቅ በሚባሉ ኬላዎች ላይ ብዙም ትኩረት እየተቸረው አለመሆኑን የሚያመላክቱ በርካታ ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ በቅርጫት ውስጥ ንብረት መሆናቸው እየታወቀ እንዴት ይጣላሉ። ስለዚህ ፍተሻ እንዲያደርግና ኃላፊነቱ የተሰጠው አካል በዚህ ዙሪያ ራሱን መፈተሽ አለበት። ስለ ጉዳዩ በቂ ግንዛቤም እንዲጨብጥ የማድረጉን ሥራ ተቋማት ሊሰሩ ይገባቸዋል።
ሌላው የዳሰሳ ጥናት አቅራቢ አቶ ተመስገን ጥጋቡ እንደሚሉት፤ የጀነቲክ ዝውውር ጉዳይ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ላይ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ አገሪቱ በፖሊሲ ደረጃ ጥብቅ ነች፤ በዚህም ከዓለም አገራት የተሻለ የብዝሀ ህይወት ጥበቃ እንዲኖሯት ሆኗል። ነገር ግን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት የሚደረገው ዝርፊያ ወይም ህገ ወጥ ዝውውር አገሪቱን ለመድኃኒትነት የሚውሉ ዕፅዋቶችን እንድታጣ፤ ብርቅየ የሆኑ እንስሳትና ዕፅዋት እንዲወድሙባት፣ ህገ ወጥ አደንም እንዲበረታታ እያደረገ ነው።
በጀነቲክ ሀብቱ ላይ ያላትን የባለቤትነት መብትም ቢሆን እንዲሁ የምታጣበት ሁኔታ ምቹ ነው፤ ስለዚህ የተያዙትን የጀነቲክ ሀብቶች መለየትና ጥብቅ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል፤ ማህበረሰቡም ሆነ ባለሙያው ስለጉዳዩ በሚገባ ማወቅና ጥበቃ ማድረግ ይኖርበታል። እያንዳንዱ ማህበረሰብም ቢሆን እንዲሁ ህገ ወጥ የጀነቲክ ሀብት ዝውውርን መቆጣጠር ህይወትን ከመጠበቅ ጋር የማይለያይ መሆኑን መረዳትና ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ያስረዳሉ።
በአንድ ኬላ ብቻ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 613 የጀነቲክ ሀብት በድግግሞሽ (57 የጀነቲክ ሀብት ዝርያዎች) መያዛቸውና ለምን ጉዳይ እንደ ሚዘዋወሩ፣ ለምን ጉዳይ እንደሚውሉና የት እንደሚሄዱ አለመታወቁ ደግሞ ምን ያህል የላላ ቁጥጥር ሥርዓት በአገሪቱ ውስጥ እንዳለ የሚያመላ ክት ነው የሚሉት አቶ ተመስገን፤ ትኩረት ለጀነቲክ ሀብት ዝውውር ይሁን የሚል መልዕክት አስተላ ልፈዋል፡፡

 

ጽጌረዳ ጫንያለው 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።