የግንባታ መጓተት በጋራ መኖሪያ ቤት Featured

10 Feb 2018

በ13 ዓመታት ውስጥ በ20/80፤ በ10/90 እና በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራሞች 178 ሺ ቤቶች ለነዋሪ ተላልፈዋል፡፡ አሁን በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም 94ሺ 144 ቤት፤ 38ሺ 240 ቤት ደግሞ በ40/60 የቤት ፕሮግራም በአጠቃላይ 132ሺ 344 ቤቶች ግንባታ ላይ እንዳሉ ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

የቢሮ ሃላፊው አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ እንደሚናገሩት፤ ቤት መገንባት ብቻ ሳይሆን በከተማው ውስጥ ሌላ ከተማ እየተቆረቆረ ነው፡፡ ቆዬ ፈጬ ብቻውን ከ60ሺ ያላነሱ ቤቶች ተገንብተውበታል፡፡ የግንባታ አካባቢዎቹ በጣም ሰፋፊና ከፍተኛ አቅም የሚጠይቁ ናቸው፡፡
በግንባታው ሂደት ከ50ሺ በላይ ዜጎች በቋሚና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ የ6 ወር አፈፃፀሙ ሲታይ፤ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር ተፈጥሯል፡፡ በፊት በተደጋጋሚ ይገለፅ የነበረው የፋይናንስ ችግር ተወግዷል፡፡ በግማሽ ዓመቱ ወደ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ጥቅም ላይ ውሏል፡፡
የፋይናንስ አጠቃቀሙ እንደሚያሳየው፤ በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል የተባለው የ40/60 በቁጥር17ሺ መኖሪያ ቤት አሁን 72 ነጥብ 8 በመቶ ተገንብቷል፡፡ 80 በመቶ ይጠናቀቃል የተባለው የ40/60ም 20ሺ 503 መኖሪያ ቤት 56 ነጥብ 4 በመቶ ተገንብቷል፡፡ በ20/80 የቤት ልማት በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል የተባለው 26ሺ 480 ቤት 80 በመቶ ተገንብቷል። ቀሪው 20 በመቶ በቀጣዮቹ ጊዜያት ይገነባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይገልፃሉ፡፡
‹‹የተያዘው ሰፊ የቤት ግንባታ ሥራ በከተማ ውስጥ ያለውን መልሶ ማልማት እንዲፋጠን ለማድረግ ያለው አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም›› በማለት የተናገሩት አቶ ይድነቃቸው ቢሮው የመምህራንን አምስት ሺ ቤቶች የማደስ እና በ10/90ም ሆነ በ20/80 ቤት ማግኘት ለማይችሉ ለከተማዋ ነዋሪዎች የከተማ አስተዳደሩ የመደበውን 350 ሚሊዮን ብር ተጠቅሞ 2ሺ ቤት ማስገንባት ተጨማሪ ሥራው እንደነበር ያብራራሉ፡፡ እነዚህ ቤቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለኪራይ የሚቀርቡ መሆናቸውን አስታውሰው፤ በተቻለ አቅም ለቤት ልማት ቢሮውም ሆነ መንግስት በከፍተኛ ትኩረት እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ያጋጠሙ ችግሮችን አስመልክቶም አቶ ይድነቃቸው ሲገልፁ፤ በ11ኛ ዙር የተላለፉት 39ሺ 249 ቤቶች መሰረተ ልማት አልተሟላላቸውም፡፡ የ40/60ው የተሻለ ቢሆንም 20/80 ላይ እና 10/90 ላይ ቤቶች ቢተላለፉም፤ነዋሪው ገብቶ በአንዳንድ አካባቢዎች መብራትና ውሃ የለም፡፡ ኮዬ ፈጬ 9ሺ908 ቤቶች በ10/90 ተሰርተው ለነዋሪው መተላለፉ ተጠቃሚዎቹን ቢያረካውም መሰረተ ልማት ባለመሟላቱ እርካታቸው መልሶ እየጠፋ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
አቶ ይድነቃቸው እንደገለፁት፤አራብሳም 20ሺ 265 ቤት፤ ቅሊንጦ ደግሞ ሰባት ሺ አካባቢ ቤቶች መሰረተ ልማት አልተሟላላቸውም፡፡ ምንም እንኳ የአፈፃፀም ችግሩ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ዓመትም ቤቶች ተጠናቀው ለነዋሪዎች ማስተላለፍ ቢቻልም፤ የመሰረተ ልማት ችግር ያጋጥማል የሚል ሥጋት አለ፡፡
የቢሮ ሃላፊው እንደሚገልፁት፤ በመልካም አስተዳደር ችግርነት ተጠቅሶ በዋነኛነት ትኩረት ከተሰጡት ጉዳዮች መካከል አንደኛው ቤት መሆኑን አስታውሰው፤ፍላጎቱና አቅርቦቱ አለመመጣጠኑ የመጣበትን ምክንያት ያብራራሉ፡፡ ስለግንባታዎች መዘግየትም ይናገራሉ፡፡
ህፃዎችን ለመገንባት ከ10 እና 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ውሃ በቦቴ እየተመላለሰ ነው፡፡ መብራት በጀነሬተር እንጂ ሃይል ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ እነዚህ በግንባታ አፈፃፀም ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉት ችግር ቀላል አይደለም፡፡ ሌላው የፋይናንስ ችግር ባይኖርም ተቋራጩ በሙሉ አቅሙ እየገባ አይደለም፡፡ ሁለትና ሶስት ህንፃ ይዞ አንዱን ብቻ ይሰራል፡፡ 30 ሰራተኛን ማሰማራት ሲኖርበት ሶስት ሰራተኛ ይዞ ይገነባል፡፡ የተቋራጭ አቅም ትልቅ ፈተና ሆኗል፡፡ በርካታዎች የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል ይላሉ፡፡
ሲታቀድ መጀመሪያውኑ የአቅም ግንባታ ፕሮግራም ተብሎ በመያዙ የተቋራጩን አቅም ለመገንባት ነበር፡፡ ሆኖም አሁን የአቅም ግንባታ ቆሟል፡፡ ተቋራጩ ለሰራተኛ ደመወዝ በወቅቱ አይከፍልም፡፡ አብዛኛው ተቋራጭ ዘንድ ያለው ተነሳሽነት አነስተኛ ነው፡፡ ተቋራጮቹ በቁርጥ ዋጋ ለቀን ሰራተኛ 50 እና 60 ብር እየተከፈላቸው ነው፡፡ ገበያው ግን እጥፍ ደርሷል፡፡ የእንጨትና የብረት ሰራተኛ ዋጋም ጨምሯል፡፡ ዋጋዎቹ ተገቢ አይደሉም እያሉ ነው፡፡ ይህ በጥናት መመለስ አለበት ተብሎ ተጀምሯል በማለት የተቋራጩን ጥያቄ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡አቅምን ማዕከል በማድረግ እና ቤቱ ሲተላለፍ ዋጋው እንዳይንር ሁለቱን ሚዛናዊ በማድረግ ስራው እንዲቀጥል የታሰበ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
አቶ ይድነቃቸው የሚያነሱት ሌላው የግንባታው መጓተት መንስኤ የግብአት ትልቅ ችግር መኖሩን ነው፡፡ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አለ፡፡ በግንባታው ላይ ላለው ብቻ 144 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በፊት ውለታ ተገብቶባቸው የነበሩ ዕቃ አቅራቢዎች ሳይቀሩ ከምንዛሬ ጭማሪው ጋር ተያይዞ የዋጋ ማሻሻያ ይደረግልን በማለት ዕቃ ማቅረባቸውን አቁመዋል፡፡ ይህም በግንባታው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ባይ ናቸው፡፡
የመሬት ጥበት በመኖሩ ባለአራት ፎቅ ቀርቶ እስከ ሰባት ወለል እየተገነባ ይገኛል፡፡40/60 ደግሞ እስከ 18ኛ ፎቅ እየተገነባ ነው፡፡ አሳንሰር(ሊፍት) ማቅረብ ግን አልተቻለም፡፡ የአገር ውስጥ አቅም ችግር አለበት፡፡ ለተላለፉት 100 ህንፃዎች 200 አሳንሰሮች ያስፈልጓቸዋል፡፡ ነገር ግን አልተገጠመላቸውም፡፡ በቀጣይ ደግሞ 2ሺ አሳንሰር የሚያስፈልጋቸው ህንፃዎች እየተገነቡ ናቸው፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሬ ላይ ከፍተኛ ዕገዛ የሚያስፈልግ መሆኑንም ነው የሚናገሩት፡፡
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፉፊ ድልጋሳ መጀመሪያ ከበጀት ጋር ችግር ነበር፡፡ አሁን ግን ችግሩ ተቀርፏል ይላሉ፡፡ 20 ቢሊዮን ብር ለበጀቱ ተመድቧል፡፡ ከክፍያ ጋር ተያይዞ ባንኮች ያዘገያሉ የተባለውም ተስተካክሏል፡፡መንግስት የቴክኒክ፣ የኦፕሬሽን እና አስተባባሪ ሶስት ኮሚቴ አቋቁሞ በትኩረት እየሰራ ነው በማለት በመንግስት በኩል ያለውን ተነሳሽነት ያብራራሉ፡፡
ሆኖም ግን በዛ ልክ ስራው እየተሰራ አይደለም፡፡ ህዝቡ ቆጥቧል፤ በቆጠበው ገንዘብ ተጠቃሚና ባለቤት መሆን ይፈልጋል፡፡ የ40/60ም ሆነ የ20/80 ቤቶች ችግራቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ በፊት ያጓትት የነበረው መሬቱን ነፃ የማድረግ እና የካሳ ክፍያ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
እንደአቶ ይድነቃቸው ሁሉ አቶ ፉፊም ሌላኛው ትልቁ ችግር የሥራ ተቋራጮች አቅም ማነስ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ተቋራጮችን እንዴት መደገፍና መከታተል እንደሚቻል መወያየት ያስፈልጋል፡፡ ሥራ ተቋራጮች መስፈርቱን አሟልተው ወደ ግንባታ የገቡ አይመስሉም፡፡ ለስራ የሚያስፈልጉ ባለሙያዎች፣ ማሽነሪዎችንና ተገቢውን ግብአት ይዞ ያለመግባት ችግር አለ፡፡ እንዲሁም ለግንባታ የተሰጣቸውንም ገንዘብ የሚገነቡበት አይመስሉም በማለት የተቋራጮችን ክፍተት ያስረዳሉ፡፡
ግንባታው በሚፈለገው ልክ እየተፈፀመ አይደለም፡፡ በተለይ በ2010 ይተላለፋሉ የተባሉት ቤቶች እንዲጠናቀቁ ከወዲሁ መሰራት አለበት ባይ ናቸው፡፡
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ዶክተር አምባቸው መኮንን፤ የሁለቱንም ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ የኢኮኖሚ አቅም በጨመረ ቁጥር ዜጎች የሚጠይቋቸው ፍላጎቶች እያደጉ ነው፡፡ በዋነኛነት የቤት ፍላጎት ሲሆን፤ ይህን ለማሳካት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ያለፉት ቤቶች ብዙ ትምህርት ተወስዶባቸዋል፡፡ በዚህ ዓመት 32 ሺ ቤቶች ይተላለፋሉ፡፡ ከሞላ ጎደል በ40/60 እና በ20/80 ይተላለፋሉ ተብለው የታሰቡት ቤቶች ብዙዎቹ ጥሩ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ ሆኖም ለውጥ ያላሳዩም ስላሉ የሚመለከታቸው አካላት መረባረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
‹‹ተቋራጮች ሥራዎችን በጥራት ጊዜውን ጠብቀው ማስረከብ አለባቸው፡፡ በሰው ሃይልም ሆነ በሥራ አመራር ብቃታቸውን ማሳደግ እና አቅማቸውን ማጎልበት ይኖርባቸዋል፡፡ ጥሩ የሥራ አመራር ብቃት እንዳላቸው ያሳዩ አሉ፡፡ በሌላ በኩል የሚጠበቅባቸውን ሥራ በጥራትና በወቅቱ መስራት ያልቻሉም አጋጥመዋል›› በማለት አንዱም የመጓተቱ ችግር የአማካሪዎችና የተቋራጮች አቅም ክፍተት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
‹‹ጊዜ ትልቅ ሀብት በመሆኑ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል›› ያሉት ሚኒስትሩ፤ ቶሎ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ በሌሎች አገራት እንደሚሰራው ሁሉ በርከት ያለ የሰው ሃይል ማሳተፍ፤ሌሊትም ጭምር መሰራት አለበት፡፡ የባንክ ባለሙያዎችም ቀድመው ግንባታውን ማየት አለባቸው ብለዋል፡፡
ተቋራጮቹ የተለያየ አቅምና ስነምግባር ያላቸው ናቸው፡፡ የፋይናንስ ችግር የለም፤ ስራቸውን ለሰሩ ይከፈላል፡፡ የመክፈል ሂደቱ የሚጓተት ከሆነ ይታያል፡፡ ሁሉም ሰው ተሳቆ እየሰራ ነው፡፡ማንም የማዘግየት መብት የለውም፡፡ ከዚህ ውጪ ተቋራጮችንና አማካሪዎችን የሚያቀጭጭ አሰራር ካለ መታየት እንዳለበት አያጠያይቅም ብለዋል፡፡
የግብአት አቅርቦት ችግር በሚል ለተነሳውም፤ ግንባታው ሰፊ በመሆኑ የሚያስፈልገው የብረት፣ የሲሚንቶ እና የጠጠር አቅርቦት በጣም ብዙ ነው፡፡ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችም አሉ፡፡ ለእነዚህ የውጭ ምንዛሬ የሚያስፈልግ በመሆኑ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ጉዳዩ ትልቅ በመሆኑ መጓተቱን ለመቀነስ የጋራ ሥራን ይጠይቃል፡፡ ሁሉም እንደራሱ ማየት አለበት፡፡ ጉዳዩ የተወሰኑ ሰዎች ተሸክመውት የሚሰቃዩበት መሆን የለበትም በማለት ሃሳባቸውን ይደመድማሉ፡፡

 

ምህረት ሞገስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።