ኅብረት ሥራ ማህበራት ለዋጋ ማረጋጋት

12 Feb 2018

በኢትዮጵያ የኅብረት ሥራ ማህበራት ታሪክ 50 ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ማህበራቱ በሥርዓት ተደራጅተው፤ በፖሊሲ ታቅፈው ሥራ ከጀመሩ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አልሆናቸውም፡፡ በአሁኑ ሰዓት የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመርና ወደ ውጭ በመላክ ለአገሪቷ ገቢ ያስገባሉ፡፡ የኅብረት ሥራ ማህበር ኤጀንሲ የኅብረት ማህበራትን እንቅስቃሴ የማጎልበት፣ የሰው ኃይል የማሰልጠን፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርፆ የማቅረብ፣ የጥናትና ምርምር ተግባራትን የማካሄድ ኃላፊነት ተሰጥቶት በአዋጅ ቁጥር 274/94 የተቋቋመ መስሪያ ቤት ነው፡፡ በዚህም በአገሪቱ ውስጥ የህብረት ስራ ማህበራት ድህነትና ኋላቀርነትን ከአገሪቱ ለማስወገድ የተነደፉ የልማት ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና እቅዶች እውን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
የኅብረት ሥራ ማህበራት ከዘይት፣ ስኳርና ዱቄት በተጨማሪ በርካታ የግብርና ምርቶችን ለተጠቃሚው ያቀርባሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን መንግሥት በድጎማ የሚያቀርባቸው እነዚህ ምርቶች ላይ የአቅርቦትና የፍላጎት ያለመጣጣም ችግር አለ፡፡ ስለሆነም አነስተኛ ገቢ ላለው ኅብረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ በማህበራት አማካይነት ያቀርባል፡፡ በመዲናዋ ከ130 የሚበልጡ ማህበራት አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባራት እንደሚስተዋልባቸውና እነዚህንም ተከታትሎ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ የኅብረት ሥራ ማህበር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር ይናገራሉ፡፡
የኅብረት ሥራ ማህበራት የአርሶና አርብቶ አደሩን ምርት ለማሳደግ የሚያስችሉ የምርት ግብአቶችን በማቅረብና የተሻለ ገበያ ዋጋ በመፈለግ የአርሶና አርብቶ አደሩን ኑሮ በመለወጥ በከተማና በገጠር የሚኖረውን ኅብረተሰብ የቁጠባ ባህል ከማዳበሩም በዘለለ ለኅብረተሰቡ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የዋጋ ንረትን ለማርገብ የኅብረት ሥራ ማህበራት የጎላ ሚና እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ አልፎ አልፎ በሚከሰተው የዋጋ ንረት ምክንያትም መሠረታዊ ፍጆታዎች ኅብረተሰቡ እያገኘ አለመሆኑን ይነገራል፡፡ የሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራትም መሠረታዊ ፍጆታዎች በተፈለገው መጠን ከኅብረት ሥራ ማህበራት እየቀረቡለት አለመሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
ማህበራቱ ለረጅም ጊዜ በሙስና መረብ ተጠልፈው ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት ግን የኅብረት ሥራ ማህበራት ከተቋቋመላቸው ዓላማ አኳያ ሕዝቡን እንዲያገለግሉና አባላቱን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ መንግሥት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው። የኅብረት ሥራ ማህበራት ዓላማቸው የሸማቾችን ፍላጎት ማሟላትና የኑሮ ውድነትን መቀነስ ነው ተብሎ ቢታሰብም በአዲስ አበባና አንዳንድ የአገራችን ክልሎች የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራት ላይ የሸቀጦች ሽያጭ የሚካሄደው በቀበሌ መታወቂያ አማካኝነት ነው። ይህ ደግሞ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡
የኅብረት ሥራ ማህበራት የአባላትን ኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርጉት የሥራ እንቅስቃሴ በየጊዜው እያደገ ይገኛል፡፡ ዘርፉን ለማጠናከር በተሰራው ሥራ ከ17 ሚሊዮን በላይ አባላት ያፈሩ ከ83 ሺ በላይ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማህበራት፣ 381 የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች እና ሦስት ክልላዊ የኅብረት ሥራ ፌዴሬሽኖች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተደራጅተው 20 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ካፒታል ማፍራትና 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ቁጠባ በማሰባሰብ ለአገሪቱ እድገት አስተዋፅኦ እያደረጉ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ኡስማን ሱሩር ይናገራሉ፡፡
በግብርናው ዘርፍ የተደራጁ ኅብረት ሥራ ማህበራት የአርሶና የአርብቶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በዘላቂነት ሊያሳድጉ የሚችሉት ለተመረተው ምርት በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም ገበያ መዳረሻቸውን በማስፋት ለአምራቹ ምርት ተመጣጣኝና ፍትሐዊ የገበያ ዋጋ ማግኘት እንዲችል ሲያደርጉ መሆኑን አቶ ኡስማን ይናገራሉ፡፡ ይህን ለማሳካት የኅብረት ሥራ ማህበራቱ የገበያ መዳረሻቸውን በአገር ውስጥና በውጭ አገራት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከኅብረት ሥራ ማህበራቱ መዳረሻዎች መካከል በዋነኝነት በከተሞች የሚገኙ ሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት፣ የግብርና ምርቶች የሚያቀናብሩ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ለአደጋ ጊዜ የግብርና ምርቶችን ከሚያከማቹ ተቋማት ጋር የሚደረጉ ትስስሮች ተጠቃሾች መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡
በኅብረት ሥራ ማህበራትና በመሠረታዊ ሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት መካከል ትስስር በመፍጠር ኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የግብርና ምርቶችን እንዲያገኝ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንና የኅብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች የግብርና ምርቶች ማቅረብ ላይ ያሉባቸውን ችግሮች በመፍታት ምርቶችን ለኅብረተሰቡ እንዲያቀርቡ ለማድረግ ኤጀንሲው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ኃላፊው ይገልፃሉ፡፡ በመሠረታዊ ሸማች ማህበራት ሲቋቋሙ በዋናነት ገበያ የማረጋጋት ሥራ ሊሰሩ እንደመሆኑ በግብርና ምርቶች ላይ የዋጋ መናር ሲፈጠር ከኅብረት ሥራ ማህበራት ጋር በመተባበር የዋጋ ማረጋጋት ሥራ እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ በዚህም ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ያስረዳሉ፡፡
የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ የግብይት ዳይሬክተር አቶ ሙሉሻው በቀለ፤ በአገሪቱ የዋጋ መናር ሲከሰት መሠረታዊ ሸቀጦችን መሠረታዊ ሸማች ማህበራቱ በራሳቸው የሚያመጡትበት ሁኔታ አለ፤ የግብርና ምርት ደግሞ ከኅብረት ሥራ ከዩኒየኖች እንደሚረከቡ ይናገራሉ፡፡ መሠረታዊ ሸማች ኅብረት ሥራ ማህበሩ ከተመደቡለት ዩኒየኖች የግብርና ምርቶችን የሚያስገባ ሲሆን፣ በዩኒየኖቹ የማይገኙ ምርቶችን ደግሞ ከክልል አምራች ማህበራት ጋር ትስስር በመፍጠር ምርት በማስገባት ለመሠረታዊ ሸማች ማህበራት ያስረክባሉ፡፡ የምርቶቹ ብዛትና የሚመጡበት ጊዜ የሚወሰነው መሠረታዊ ማህበሩ በሚያቀርበው ጥያቄ መሠረት ነው፡፡ መሠረታዊ ሸማች ማህበሩ በማንኛውም ሰዓት ምርት እንዲቀርብለት ጥያቄ ሲያቀርብ የኅብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች የማቅረብ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
በአስሩም ክፍለከተሞች ምርት የሚያቀርቡ የተመደቡ ዩኒየኖች አሉ፡፡ ዩኒየኖቹ በሥራቸው ላለው መሠረታዊ ሸማች ማህበር ምርት ያቀርባሉ፡፡ መሠረታዊ ሸማች ማህበሩ አተር፣ ስንዴ፣ ባቄላና ጤፍ ይህን ያክል ኩንታል ብሎ ሲያሳውቅ ምርቶቹ በፍጥነት እንደሚቀርቡ ያመለክታሉ፡፡ ዩኒየኖቹ የገበያ መጨመር ቢከሰት እንኳን ቀድሞ ሲያቀርቡበት በነበረው ዋጋ እንጂ ጭማሪ እንደማያደርጉ የሚጠቅሱት አቶ ሙሉሻው፤ በምሳሌነትም በጥር ወር ላይ የተገዛው ምርት የካቲት ወር ላይ መጨመር ቢያሳይ ከዩኒየኖቹ ማቅረቢያ ዋጋ እንደማይጨምር ይጠቁማሉ፡፡ ምርቶችን ለመሸጥ ቀድሞ በተተመነው ዋጋ ነው የሚሸጠው፡፡ ይህም የዋጋ መጨመር ሲከሰት ለማረጋጋት በሚደረጉ ሥራዎች አጋዥ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በመሠረታዊ የሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት ያሉት ችግሮች በዋነኝነት በተገቢው መልኩ ለኅብረተሰቡ የሚፈልገውን ምርት አውቀው ለዩኒየኖች ምርት እንዲመጣላቸው ጥያቄ እንደማያቀርቡና እዚህ ላይ ክፍተት እንዳለ ይጠቁማሉ፡፡ ይህን ደግሞ በቀጣይ የማስተካከልና የማረም ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እየተሰራ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አዲስ አደረጃጀት በመፍጠር እስከ ወረዳ ድረስ የኅብረት ሥራ ማህበር የሚያጠናክሩ ጽሕፈት ቤቶች ተከፍተዋል፡፡ ጽሕፈት ቤቶቹ ደግሞ በየመሠረታዊ ሸማች ማህበሩ የግብርና ምርቶች ሕዝቡ በሚፈልገው መልኩ መኖር አለመኖራቸውን ይቆጣጠራል፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ሁሉም ጋር እኩል የግብርና ምርቶች ተደራሽ የሚሆኑበት ዕድል እየፈጠረ እንደሚገኝ ያመለክታሉ፡፡
እንደ አቶ ሙሉሻው አባባል፤ ከዩኒየኖች የሚመጣው ምርት በቀጥታ ለኅብረተሰቡ እንዲደርስ ይፈለጋል፡፡ ማንኛውም ሰው ምርቱን ሄዶ ማግኘት ይችላል፡፡ አብዛኛው ምርቶች በመጋዘን ውስጥ ቢኖሩም ሰው እንዲገዛ የማድረግ ሥራ አናሳ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ አካባቢ ያሉት ችግሮች እንዲቀረፉ የጤፍ ዘሮችን በየዓይነታቸው ስም ተፅፎበት በኪሎ በየሱቁ እንዲሸጥ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ቀደም ብሎ ኅብረተሰቡ በወፍጮ ቤቱ ብቻ ነበር ጤፍ ገዝቶና አስፈጭቶ የሚጠቀመው፡፡ አሁን ግን ይህን ባህል ለመቀየር ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን ያክል የተፈጨ ጤፍ መግዛት እንዲችል ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ያመለክታሉ፡፡
በአጠቃላይ የኅብረት ሥራ ማህበራት ገበያን ለማረጋጋትና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የሚጫወቱት ሚና የላቀ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ዘርፉ እስከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ድረስ ወርዶ የሚሰጡ የአገልግሎቶች ላይ የሚታዩ ችግሮችን መፈተሽ ይጠበቅበታል፡፡ ምክንያቱም ኅብረተሰቡ በሸማቾችና ዩኒየኖች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግሮች እንዳሉ በተደጋጋሚ ሲያነሳ ይሰማል፡፡ ስለዚህ የኅብረት ሥራ ማህበሩ የያዘውን ዓላማ እንዲያሳካ ከኅብረተሰቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከርና በውስጥ የሚታዩ የአሠራር ክፍተቶችንም ፈትሾ ማስተካከል ይጠበቅበታል፡፡

መርድ ክፍሉ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።