እድገቱን እንዲደግፍ ተደርጎ መቃኘት ያለበት የፋይናንስ ሪፖርት ስርዓት

13 Feb 2018

በኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና ሪፖርት ኦዲት ቁጥር 847/2006 አንቀፅ አራት አንድ ላይ እንደተመለከተው ቦርዱ በሚኒስተሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 332/2007 የተቋቋመ መንግስታዊ መስሪያ ቤት ነው። ተቋሙ መንግስት በአገሪቱ የግልና የመንግስት ድርጅቶች ላይ ተፈፃሚ እንዲሆን ያወጣው የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ አዋጅን መሰረት በማድረግ ነው የተቋቋመው።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከቦርዱ ዋና ዳይሬክተር አማካሪና የፅህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ደመላሽ ደበሌ ጋር የፋይናንስ ሪፖርት አቀራርብ ስርዓትን በአግባቡ መከወን ስላለው ፋይዳ፤ አጠቃላይ ስለ ቦርዱ ተግባራትና እያጋጠሙ ስላሉ ተግዳሮቶች ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ከአዋጁ በፊት የአገሪቱ ፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ የነበረው ገፅታ
ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት በመንግስትም ይሁን በግሉ ዘርፉ ያሉ ድርጅቶች ሊከተሉት የሚገባ ዝቅተኛ ወይንም ተቀባይነት ያለው ወጥ እና ማንኛውም ሰው በቀላሉ የሚረዳው የሪፖርት አቀራረብ ስርዓት አልነበረም። አንድ ወጥ የሆነና የአገሪቱን እድገት ታሳቢ ያደረገ ወቅቱ በሚጠይቀው ደረጃ ዘመናዊ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ስርዓትን የሚመራ ህግም አልነበረም። ያሉትም ህጎች ቢሆኑ ድርጅቶች በተመቻቸው መንገድ የሚያወጧቸው ናቸው።
አቶ ደመላሽ ለአብነትም ታክስን በመውሰድ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ስለሚጠይቀው ሪፖርት ያብራራሉ። ሪፖርቱ ወጥ በሆነ እና ተቀባይነት ባለው መልኩ ተሰርቶ የሚቀርብ ባለመሆኑ መንግስት ሊሰበስብ የሚገባው ግብር በአግባቡ እንዳይሰበስብ አድርጎታል። ግብሩ አንዱ ላይ ከፍተኛ ሌላው ዘንድ ዝቅተኛ የሚሆነውም በዚህ ምክንያት ነው ይላሉ።
ከዚህ በተጓዳኝ ቁጥሮች ትመለከታለህ፤ ከቁጥሮቹ ጀርባ ያለውን አታውቅም። ይህን ያህል ሃብት አለኝ ይላል። ይሁንና በእርግጥ ሃብቱ ያለበትን ደረጃ፣ ጥቅም የሚሰጥ ነው ወይንስ የማይሰጥና በብልሽት የተቀመጠ የሚለው የሚታይበት ሁኔታ የለም።
የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ስርዓት በአግባቡ መመራት እና የቦርዱ መቋቋም ያለው ፋይዳ
አቶ ደመላሽ እንደሚሉት፤ ምቹ የቢዝነስ አካባቢ ለኢኮኖሚ ማደግ ከፍተኛ ሚና አለው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገና አገሪቱም ወደ ዓለም ገበያ እየገባች ነው። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በእጅጉ እየጨመረ ነው። ይህ ለኢኮኖሚው ትልቅ ሃይል ቢሆንም በአግባቡ መቆጣጠርና መምራት ካልተቻለ ችግር ይዞ ይመጣል።
እንደ አገር ከኢንቨስትመንት ማግኘት ያለብንን ገቢ እንድናገኝ የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ከሌለን ባለሃብቶቹ ያመጡትን መዋለ ንዋይ መልሰው የሚወስዱበት ሁኔታ ይፈጠራል። በመሆኑም የፋይናንስ ሪፖርት ስርዓታችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚ እድገቱን መደገፍ በሚችል ደረጃ መቃኘት ይኖርብናል፡፤
ሙስና የሚመጣው ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት ከሌለ ነው የሚሉት አቶ ደመላሽ፣ የቁጥጥር ስርዓት ከሚገለፅባቸውና የሙስናን በር ከሚያጠቡ መንገዶች አንዱ ጠንካራ የፋይናንስ የአሰራር ስርዓት መሆኑን ያብራራሉ። የፋይናንስ የአሰራር ስርዓት በጠነከረ ቁጥር የግለሰቦች መደበቂያ እያነሰና እየጠፋ ይመጣል ይላሉ። ለዚህም ቦርዱ ትልቅ አገራዊ ፋይዳ እንደሚኖረው ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አቶ ደመላሽ ማብራሪያ፤ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ታላላቅ አገራዊ ግቦች ፣ ሜጋ ፕሮጀክቶች ተቀርፀዋል። ከዚህ በተጓዳኝ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ይታሰባል። ይህ ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ የአገር ውስጥ ሃብት ማፍራትና በአግባቡ መጠቀምን ይጠይቃል። በዚህ መልክ ለማንሸፍነው ደግሞ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ወሳኝ ነው።
እነዚህን ለማግኘት በመሰረታዊነት መከናወን ካለባቸው ተግባራት መካከል የአገር ውስጥ ሃብትን ለማሰባሰብ የታክስ አሰባሰብ ስርዓቱን ማጠናከር፣ ጥራት ያለው አስተማማኝ፣ ግልፅ፣ ወጥነት ያለውና ሁሉም በቀላሉ ሊረዳው የሚችል የፋይናንስ ሪፖርት ማቅረብ የሚሉት ይገኙበታል። ቦርዱ ይህ እንዲመጣ ይሰራል።
የፋይናንስ ሪፖርት እና ኦዲት አቀራረብ አዋጅ እነማንን ይመለከታል?
አዋጁ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን እና በመንግስት በጀት የሚተዳሩ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን አይመለከትም። በንግድ ተግባር በተሰማሩ የግልም ይሁኑ የመንግስት ድርጅቶች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ማህበራትና ተመሳሳይ ሀላፊነት ያለባቸው ድርጅቶችንም ይመለከታል።
የቦርዱ ሃላፊነት እስከ ምን ድረስ ነው ?
እንደ አቶ ደመላሽ ገለጻ፤የመጀመሪያው ተግባሩ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎችን ማውጣት ሲሆን፣ ከእነዚህም አንዱ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃ ነው። ሁለተኛው የኦዲት ጥራትና የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብና አዘገጃጀት ግምገማና ክትትል ማድረግ ነው፤ ይህም በደረጃዎች መሰረት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን መከታተል ማለት ነው። የሙያ ትምህርት ስልጠናና ማጎልበቻ፤ የብቃት ማረጋገጥ እና እውቅና የመስጠት ተግባር ሌላኛው ነው። የምርመራና ህግ የማስከበር ተግባራትንም ያከናውናል፤ ይህም አንድ አራተኛ የሚሆነውን የአዋጁን ክፍል ይይዛል፡፡
በተቀመጠው ደረጃና ህግ መሰረትም እያንዳንዱ የንግድ ድርጅት እንደአቅምና ደረጃው የፋይናንስ እና የኦዲት ሪፖርቱን ለቦርዱ ያቀርባል። የቦርዱ ባለሙያዎች የቀረቡላቸውን ማስረጃዎች አገሪቱ ባስቀመጠችው የሪፖርት አቀራረብ ደረጃ መሰረት የተሰራ መሆኑን ይገመግማሉ፤ ያረጋግጣሉ። ሪፓርቱ ደረጃውን ካልተከተለ እንዲያሻሻሉ ጊዜ ይሰጣቸዋል። ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆኑ በወንጀል ይጠየቃሉ፤ አስተዳደራዊ እርምጃም ይወሰድባቸዋል፡፡
የአዋጁ መተግበር ለውጥ ያመጣል
ቦርዱ በተለይ ወቅቱ የሚጠይቃቸው ዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎች በአግባቡ እንዲተገበሩ ሲያደረግ ከፍተኛ ጥራት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት መውጣት ይጀምራል። የሂሳብ መረጃዎች የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው ይወጣሉ።
እንደ አቶ ደመላሽ ገለጻ፤ ይህ ከግብር አንጻር ቢታይ የአንድን ድርጅት ትክክለኛ ሃብትና እዳ እስከዛሬ ካለው በተሻለ ሁኔታ ለማወቅ ያስችላል። ምን ያህል መክፈል እንዳለበት የድርድር ጉዳይ አይሆንም። ምክንያቱም ደረጃዎቹ በግልፅ እንዲያስቀምጥ የሚጠይቁት አለና።
ይህን ተከትሎ ስለመሰራቱ ደግሞ ቦርዱ ክትትል ይደርጋል። እያንዳንዱ ድርጅት ለገቢዎች እንዲሁም ለባንክ ብድር የሚያስገባው ቦርዱ ዘንድ ባስመዘገበው የፋይናንስ መግለጫ መሰረት ነው። እንደ ከዚህ ቀደሙ ለባንክ ብድር ሲፈለግ ትርፋማ ፣ ለገቢዎችና ጉምሩክ ሲፈልግ እንደከሰረ አርጎ የሚያሳየው አካሄድ አሁን ቦታ አይኖርም።
ይህ መግለጫ የሚመዘገበውም በቦርዱ ነው፡፡ ወደ ገቢዎች ታክስ የሚወሰድበት መግለጫ ቦርዱ በመዘገበው መሰረት የሚከናወን ይሆናል። እንደ አስፈላጊነቱ የሚገለባባጥ ነገር አይኖርም። ከዚህ ቀደም አንድ ቢሊየን ብር የሚያወጡ ማሽኖችም ሆነ ሌሎች ቁሳቁስ አሉኝ በሚል ብድር መውሰድ ይቻል ነበር፤ አሁን መግለጫዎችን ማቅረብ የግድ በመሆኑ አሉኝ የሚባሉ እሴቶች ተገምገመው የሂሳብ መግለጫ ውስጥ የማይገቡ ከሆነ አበዳሪዎች ይጠነቀቃሉ።
ከዚህ ቀደም ባለሙያዎች ሂሳብ ሲያዘጋጁ አንዳንድ ችግሮች ቢከሰቱ ድርጅቱ አልያም ባለቤቱ ይጠየቃል እንጂ ባለሙያው ላይ ተጠያቂ አይሆንም፤ አሁን የሂሳብ ስራ መስራት ያለበት ማነው? የሚለው ደረጃዎችና ዝርዝር መመዘኛዎች ስለተቀመጡለት የሂሳብና የኦዲት አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች እነማን ናቸው? ምን አይነት የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ ሊኖራቸውስ ይገባል? የሚለውም ተቀምጧል። ከደረጃ ውጪ የሰራ ካለም በግለሰብ ደረጃም እርምጃ ይወሰዳል በማለት አቶ ደመላሽ ያብራራሉ።
አቶ ደመላሽ እንደሚሉት፤ ከዚህ ቀደም የንግድ ድርጀቱ ባለቤት እንደዚህ አድርገህ አዘጋጅልኝ ብሎ የሚያዝበት ሁኔታ ነበር፤ አሁን ደረጃው በሚጠይቀው አግባብ እንጂ ነጋዴው በፈለገው አይፈጸምም። ባለሙያዎች በፈለጉት ስፍራ ሆነው በተጠየቁት መሰረት የሚሰሩበት መንገድ እንዲቀር እየተደረገ ነው። አንዱ ቢሮ ከፍቶና ብዙ ባለሙያዎች ቀጥሮ ለመንግስት ተገቢውን ግብር እየከፈለ ሌላኛው በተቃራኒ የሚሰራበት ሁኔታ መቅረት ይኖርበታል። እያንዳንዱ ባለሙያ ተመዝግቦ በተደራጀ መልኩ ቢሮ ከፍቶ እንዲሰራና የሰራበትን የተሟላ መረጃ እንዲይዝ በአጠቃላይ አገር፤ ባለሙያ እና ድርጀቶች ተገቢውን ጥቅም የሚያገኙበት አሰራር እንዲመጣ እየሰራን ነው።
ለቦርዱ የተሰጡት ተግባራት በማስፈፀም ረገድ የባለሙያ አቅም እንዴት ይገለፃል?
በአገራችን ውስጥ እነዚህን በተለይ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎችን ለመተግበር የሚያስችል በቂ እና አቅም ያለው ባለሙያ የለም። ስለ ሙያው ያለው ግንዛቤ በጣም ውስን ነው። እያንዳንዱ አካውንታንት በብሄራዊ ኢኮኖሚው ላይ ያለው አስተዋፆኦ አይታወቅም።
የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎችም ስለዓለም አቀፍ ደረጃዎች አልተማሩም ። ተመራቂዎቹ ስለ ዓለም ዓቀፍ ደረጃዎች እንዲያውቁ ፣ትምህርት ተቋማት ያሉትም በቂ ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ ትልቅ ስራ ይጠይቃል። በመሆኑም ከፍተኛ የትምህርትና ማስልጠኛ ተቋማት ገበያው የሚፈልገውን የሰው ሃይል እንዲያምርቱ፤ ትምህርቱም በስርዓተ ትምህርት እንዲካታትና በዓለም ዓቀፍ ደረጃዎች እንዲቃኝ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ።
በእርግጥ በአሁኑ ወቅት ማንኛውም ሰው መሰልጠን ቢፈልግ በአቅራቢያው በሚገኝ ዩኒቨርሲቲና የግል ስልጠና ተቋም መሰልጠን ይችላል። በዚህም ባለሙያዎቹ ለዓለም ዓቀፍ መስፈርቶች ያላቸው ግንዛቤ እያደገ ነው። የማሰልጠኛ ተቋማትም ዓለም ዓቀፍ መስፈርቶቹን መሰረት ያደረገ ስልጠና መስጠት መጀመራቸውን የሚያበስር ማስተወቂያ እየሰሩ ናቸው።
በማስፈፀም ረገድ የክልሎችና የፌዴራል መንግስት ግንኙነት
አቶ ደመላሽ በፋይናንስ አቀራረብና የኦዲት ሪፖርት አዋጁ ላይ የተመለከተውን ጠቅሰው እንዳሉት ፤አዋጁ በመላ አገሪቱ ተፈፃሚ ይሆናል፤ አዋጁን ለማስፈፀምም ቦርድ እንደሚቋቋም በተገለጸው መሰረት ቦርዱ ተቋቁማል፤ ቦርዱ እንዲያስፈጽም ከተሰጡት ተግባራት መካከል የሂሳብና የኦዲት ባለሙያዎች የሙያ ነፃነትን ማስጠበቅ የሚለው ይገኝበታል። ይህም ወደ ሙያው ማነው መግባት ያለበት? የሚለውን ስለሚያካትት ለዚህ መመዘኛ በማስቀመጥ ለሚያሟሉ ፈቃድ የመስጠት ሃላፊነት ለቦርዱ ተሰጥቷል።
በህገ መንግስቱ የፌዴራልና የክልል መንግስታት በማለት ሁለት እርከኖች አሉ። የክልል መንግስታት በክልላቸው ውስጥ እንዲሰሩ የተፈቀደላቸው ተግባር ያለ ሲሆን የክልል ምክር ቤቶች ለክልል ዋና የኦዲት መስሪያ ቤቶች የኦዲትና የሂሳብ ሙያን የመቆጣጣር ስልጣን ሰጥተዋቸዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር የፋይናንስ ሪፖርት አዋጁ ሲወጣና ቦርዱ ሲቋቋም ይህን ስራ አቁሟል። በተወሰኑ ክልሎች ግን አይሆንም፤ ህገ መንግስቱ በሚፈቀድው መሰረት የክልሉ ምክር ቤት ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሲቋቋም ለዋና ኦዲተር የሰጠው ስራ ነው። ፈቃድ መሰጠት ደግሞ በክልል ደረጃ የሚሰራ ስለሆነ ህገ መንግስታዊ መብታችን ይነካል። ስለዚህ ማስተካከያ መደረግ አለበት የሚል አጃንዳ አነሱ። ባለሙያዎችን ስንመዘግብ ከተወሰኑ ክልሎች መጥተው መመዝገብ አልቻሉም። ይህ ስራ የእኛ ስለሆነ በእኛ ነው የሚመራው የሚል አዝማሚያ ነበር። አሁን እነዚህ አዝማሚያዎች እየቀነሱ ሄደው ችግሩን ወደ መፍታት እየደረስን ነው።
ይህን ጥያቄ ለማስተናገድ መድረኮች ተዘጋጅተው፤ በመንግስትና በከፍተኛ ደረጃ ምክክር ተደርጎ የአዋጅ ማስተካከያ ተዘጋጅቶ ለሚኒስተሮች ምክር ቤት ተልኳል።በእርግጥ ይህ ችግር ለቦርዱ ትልቅ ፈተና እና እንቅፋት ሆኖበት ነበር።

ታምራት ተስፋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።