ዘላቂ የግብርና-ኢንዱስትሪ ትስስር ለግብርናው መዋቅራዊ ሽግግር Featured

12 Mar 2018

ግብርና የሃገራችን የኢኮኖሚ መሰረት ሆኖ ለዘመናት ኖሯል፡፡ ያም ሆኖ ግን ዘርፉ የሚፈለገውን ያክል ውጤታማ ሊሆን አልቻለም፡፡ በዚህ የተነሳም ዘርፉ በሚጠበቀው ልክ ዜጎችን ከድህነት ለማላቀቅ አልቻለም፡፡ ይሄን በመገንዘብም ግብርናው የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ከኢንዱስትሪው ጋር ማስተሳሰር አስፈላጊ ሆኖ ታምኖበት ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ በዚህም መሰረት እስካሁን በተከናወኑ ስራዎች ለውጦች እየታዩ ሲሆን፤ የግብርናውን መዋቅራዊ ሽግግር ከማረጋገጥ አኳያ በግብርናውና በኢንዱስትሪው መካከል የጠበቀ ትስስር በመፍጠር ሁለቱ እየተመጋገቡ በአገሪቱ ኢኮኖሚ የድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለድርሻዎች ይናገራሉ፡፡
አቶ ካሳሁን ገብረጊዮርጊስ የስኳርና ጣፋጭ አምራቾች ማህበር ዋና ፀሐፊ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በግብርናውና ኢንዱስትሪው ትስስር ያለና ተመጋጋቢ መሆናቸውን መገንዘብ ቢቻልም እስካሁን ባለው ሁኔታ የሁለቱ ትስስር ብዙ አልተሰራበትም፡፡ ሆኖም ኢንዱስትሪው ሊለማ ካስፈለገ ግብርናው መዘመን አለበት፤ ግብርናው እንዲዘምንም ኢንዱስትሪው የቴክኖሎጂ ግብዓት መስጠት፤ ከአርሷደሩ ጋርም ያለው ትስስር መጠንከር አለበት፡፡ ምክንያቱም ዛሬም ድረስ ከአዲስ አበባ በ50 ኪሎ ሜትር ዙሪያ በባህላዊ መንገድ የሚያመርቱ አርሷደሮች አሉ፤ ሁለት አይነት የመሬት ማዳበሪያዎች ብቻም ናቸው ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት፡፡ በመሆኑም በግብርናውና ኢንዱስትሪው መካከል ያለውን ትስስር ከማጠናከር አኳያ፣ ከአርሷደሩ ፍላጎት ጋር አዛምዶ በመስራት ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ግብርናው ኢንዱስትሪውን ሊመግብ የሚችልበትን አቅም መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ኢንዱስትሪው ግብርናው የሚያወጣውን ምርት ለመቀበል ብቻ ሳይሆን ግብርናው የሚፈልገውን ግብዓት ለማግኘት የሚችልበትን እድል መፍጠር ይገባል፡፡ ለዚህም ህብረተሰቡ፣ ባለሃብቱና መንግስት የሚጠበቁባቸውን ኃላፊነቶችን በቁርጠኝነት መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
ይሄንን ሀሳብ በመጋራት አገሪቱ የምትከተለውን የኢኮኖሚ እድገት አቅጣጫ መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከሊፋ ሁሴን ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ እስካሁን ባለው ስራ በኢንዱስትሪ ግብርና ትስስሩ ላይ መሻሻሎች ያሉ ቢሆንም መሻሻሎቹ ግን መሰረታዊ አይደሉም፡፡ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ሆነው አለመሄድ ደግሞ የዚህ አንድ ማሳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ፣ አንድም የግብርናው ምርትና ኢንዱስትሪዎች ያሉበት ቦታ መራራቅ ውጤት ሲሆን፤ ይህ ከግብይት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲፈጠሩ በር ከፍቷል፡፡ ከመብራትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ጋር በተያያዘ ያለው ክፍተት ሌላው ችግር ሲሆን፤ ግብርናው በተለምዷዊው መንገድ መከናወኑም ተጨማሪ ችግር ነው፡፡
እንደ አቶ ከሊፋ ገለጻ፤ የግብርና ምርቱ ያለው ወደገጠራማ የአገሪቱ ክፍል ሲሆን፤ በአንጻሩ ኢንዱስትሪዎቹ በአብዛኛው በአዲስ አበባ እና አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ናቸው፡፡ ይሄም አርሶ አደሩ በቀጥታ ምርቱን ወደ ኢንዱስትሪ ማቅረብ የማይችልበትን ሁኔታ በመፍጠሩ በመሃል ያሉ ደላሎች ከፍተኛውን ጥቅም የሚያገኙበት፤ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ግን ተገቢውን ጥቅም እንዳያገኝ፤ ኢንዱስትሬዎችም የጥሬ ምርት ዋጋ ውድ እየሆነባቸው በዓለም ገበያ እንዳይወዳደሩ አድርጓቸዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ከመፍታት አኳያ የግብርና ምርቱ ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ኢንዱስትሪውን የመፍጠር ስራ ተጀምሯል፡፡ የዚህ ተግባር አካል የሆነው የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪያል ፓርኮችም በሰብልም ሆነ በእንስሳት የየአካባቢን የምርት ጸጋን መሰረት አድርገው የሚተገበሩ ናቸው፡፡ ይሄም አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ ምርቱን በተሻለ ዋጋ በቀጥታ ለኢንዱስትሪዎቹ በማቅረብ ለተሻለ ምርታማነትም እንዲነሳሳ ያደርገዋል፡፡ የመሰረተ ልማቶች ችግርንም ያቃልላል፡፡ ኢንዱስትሪውም በተሻለ ዋጋ ገዝቶ ምርታማነቱን እንዲያሳድግና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡ እነዚህ ፓርኮች ወደስራ ሲገቡም በኢንዱስትሪውና በግብርናው መካከል ያለውን የላላ ትስስር በመቀየር ወደተጠናከረ ደረጃ ያደርሱታል፡፡
አቶ ከሊፋ እንደሚናገሩት፤ ኢንዱስትሪውና ግብርናው ባልተሳሰሩበት ሁኔታ አርሶ አደሩ ለምርቱ ገበያ፤ ኢንዱስትሪውም ለምርቱ ግብዓት ማጣቱ የማይቀር ነው፡፡ ችግሮችን መፍታትና በታሰበው መልኩ መሄድ ካልተቻለ ይሄው ችግር የሚቀጥል ይሆናል፡፡ በመሆኑም ለአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት ማደግ በሰብሉ በእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር፣ በእንስሳቱ ደግሞ የእንስሳትና ዓሣ ኃብት ሚኒስቴር እየሰሩበት ነው፡፡ በመሆኑም ይሄን ችግር ይፈታሉ ተብሎ እየተከናወኑ ያሉ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ስራ ውጤታማነት በትኩረት መስራት ከሁሉም ባለድርሻ ይጠበቃል፡፡
የእንስሳትና ዓሣ ኃብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ምስራቅ መኮንን በበኩላቸው፣ በግብርናው ዘርፍ ዘመናዊ አለመሆንና በዚህም የሚጠበቅበትን ድርሻ በሚፈለገው ልክ አለመወጣት ላይ የተነሱ ሀሳቦችን ይጋራሉ፡፡ የእንስሳት ዘርፉን በማሳያነት አንስተው እንደሚያስረዱትም፤ እስካሁን የእንስሳት ሃብቱ ሲለማ የነበረው በባህላዊና ልማዳዊ በሆነ መልኩ ነው፡፡ የሚረቡትም ለገበያ ተብሎ ሳይሆን ግብርናውን ለመደገፍና አርብቶ አደሩም ኑሮውን በዛ ላይ ለመመስረት ግድ ስለሆነበት ነው፡፡ ይሄም ሆኖ ግን የእንስሳት ኃብቱ በአገር ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ድርሻ እያበረከተ ነው፡፡ ሆኖም የተለመደውን ስርዓት መቀየርና ዘመናዊ የአረባብ ስርዓቶችን ለአርብቶ አደሩ በማስተማር ለገበያ የሚያመርት አርብቶ አደር ለመፍጠር እየተሰራ ነው፡፡ በሌላ በኩልም በእንስሳት ኃብት ልማቱ የተለያዩ ባለሃብቶች በየመስኩ ገብተው እንዲሰሩና ኢንዱስትሪውን ሊመግቡ በሚችሉበት አግባብ ማልማትና መጠቀም እንዲችሉ ለማድረግም የተጀመሩ ስራዎች አሉ፡፡ ለዘርፉ የላቀ አስተዋፅዖም የአደረጃጀት፣ የአሰራርና የሕግ ማዕቀፎች ጭምር ፈትሾ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት በሚያስችል አቅጣጫ እንዲመራ እየተደረገ ነው፡፡
እንደ ዶክተር ምስራቅ ገለጻ፤ የእንስሳት ሃብት ልማቱን ምርትና ምርታማነት ከማሳደግም ሆነ የኢንዱስትሪ መጋቢነቱን ለማረጋገጥ የመኖ ልማት፣ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻልና የእንስሳት ጤናን መጠበቅ አንኳር ተግባራት ናቸው፡፡ ግብርናው ኢንዱስትሪውን መደገፍ አለበት ሲባልም፤ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት በዋነኛነት የሚመሰረተው በግብርናው ላይ በመሆኑ ግብርናን ማዘመን ማለት የኢንዱስትሪ ስራውን ማሳለጥ ነው፡፡ በመሆኑም የእንስሳት ኃብት ልማቱ ላይ ትኩረት ማድረጉ የኢንዱስትሪ ልማቱንም የሚያዘምን፤ ፈጣን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥም እድል የሚሰጥ ነው፡፡ በዚህ አንጻር በዋናነት በአራት ክልሎች ላይ ተግባራዊ ከተደረጉት የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ ልምዶችን በመውሰድ በሌሎች አካባቢዎችም እንዲስፋፉ ይደረጋል፡፡ እነዚህ ፓርኮችም ከአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ግብዓት የሚፈልጉ እንደመሆናቸውም የግብርና ልማቱ ከሌለ ኢንዱስትሪው ባዶ ቆርቆሮ ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡ ስለዚህ ሁለቱ ተሳስረው መሄድ ይገባቸዋል፡፡ ለዚህም ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲሁም ከእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሥራዎች በጋራ እየገመገሙና እየመሩ ነው፡፡ በሂደቱም ችግሮችን ከማቃለል አኳያ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ መሰረቶች ከአሁኑ ማኖር ተጀምሯል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዴኤታው ዶክተር መብራህቱ መለስ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪው ለኢትዮጵያ መዋቅራዊ ሽግግር እምብርት እንደመሆኑ በአሁኑ ወቅት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በመንግስትም ሆነ በባለሃብቶች እየለሙ ነው፡፡ በመንግስት ከሚለሙ 17 ፓርኮች ውስጥ አራቱ ተግባራዊ የተደረጉ ሲሆን፤ ከመንግስት ባለፈ በባለሃብቱ የለሙ፣ እየለሙ ያሉና በቀጣይ ወደስራ ለመግባት ቅድመ ሁኔታዎችን እያጠናቀቁ ያሉ የሰብልም ሆነ የእንስሳት ሃብቱን በግብዓትነት የሚጠቀሙ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች አሉ፡፡ በመሆኑም መንግስት እነዚህ ፓርኮች እንዲለሙና የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ፣ ኢንዱስትሪውም ግብርናውን ይዞ እንዲነሳ ተመጋግቦ እንዲጓዝ ይሰራል፡፡
እንደ ዶክተር መብራህቱ ገለጻ፤ የተቀናጀ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪውን እድገት የሚወስነው ግብርናው ቢሆንም፤ አሁን ባለው ሁኔታ ግብዓት በብዛትና በጥራት ባለመኖሩ ግብርናው ኢንዱስትሪውን ያለመመገብ ችግር ይስተዋልበታል፡፡ ለአብነት፣ የምግብ ዘይት አሁንም ከውጭ ነው እየገባ ያለው፤ በአንጻሩ አገሪቱ ለዘይት ምርት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን ምርት የምታመርትበት ሰፊ አቅም አላት፡፡ ለግብርናው እድገትና ትራንስፎርሜሽንም ግብርናውን መካናይዝድ ማድረግ፣ ከዝናብ መላቀቅና መስኖ መጠቀም፣ የኤክስቴንሽን አቅጣጫው ለኢንዱስትሪ በሚሆን መልኩ እንዲቃኝ ማድረግ፣ መሰረተ ልማቶችን ማሟላት እንዲሁም ግብርናው ከኢንዱስትሪው ጋር ያለውን ቁርኝት ማጠናከር የቀጣይ ትኩረቶች ናቸው፡፡ ይሄም በኢንዱስትሪውና ግብርናው መካከል ቀጣይነት ያለው መመጋገብን የሚፈጥር ዘላቂ ጋብቻ የሚመሰርት ሲሆን፤ ይህ መመጋገብ ሲኖር ግብርናው ገበያን ሳያስብ ምርቱን ብቻ በስታንዳርድ እንዲያመርት፤ ኢንዱስትሪውም ስለ ጥሬ እቃ ሳይሆን ጥራት ያለው ምርት አምርቶ ተወዳዳሪ የሚሆንበትን መንገድ ብቻ በማሰብ የጋራ ተጠቃሚነትና እድገት ላይ ተመስርተው እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል፡፡

ወንድወሰን ሽመልስ 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።