«ፋብሪካዎች የሚወስዱትን የግብአት ብድር በወቅቱ ባለመመለሳቸው ድርጅቱ እየተፈተነ ነው» - አቶ መላኩ ታዬ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአት ልማት ድርጅት የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ሥራ አስፈፃሚ Featured

13 Mar 2018

ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የሚደረገውን ሽግግር በረዥም ጊዜ ሂደት እውን ለማድረግ እንዲሁም በአፍሪካ ቀዳሚ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማእከል ለመሆን እየሰራች ትገኛለች። የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን የኢንዱስትሪ ግብአት አቅርቦት ማረጋገጥ ሌላኛው የቤት ሥራ በመሆኑ እኩል ትኩረት እና ሰፊ ጥረት ይፈልጋል። ለዚህም ሲባል መንግስት በ2006 ዓ.ም በቀድሞ የሸቀጦች ጅምላ ንግድ እና አቅራቢ ድርጅት ወይም ጅንአድ ላይ የተልእኮና ስያሜ ለውጥ በማድረግ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ተብሎ እንዲቋቋም ማድረጉ ይታወቃል። የድርጅቱ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ታዬ ድርጅቱ ስለተቋቋመበት ተልእኮ፣ወቅታዊ አፈፃፀምና ስላሉበት ችግሮች ከአዲስ ዘመን ጋር ያደረጉትን ቃለ-መጠይቅ ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ሲቋቋም የተሰጡትን ዓበይት ተልእኮዎችንና ለዘርፉ ያበረከተውን ጠቀሜታ ቢያብራሩልኝ ?
አቶ መላኩ፡- መንግስት ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር የሚደረገው መዋቅራዊ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ግንባር ቀደም የሆነች አገር ለመፍጠር እና ማኑፋክቸሪንግ በአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚጫወተውን ሚና ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል። በመጀመሪያውም ሆነ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ዋነኛው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማነቆ የግብአት እጥረት ነው። ብቸኛው ችግር ግን አይደለም። ስለዚህ ዘርፉ በአለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዳይሆን የግብአት እጥረት ቁልፉ ማነቆ እስከሆነ ድረስ መንግስት ችግሩን ከመሰረቱ ይፈታልኛል ብሎ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ድርጅትን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 328/2006 መሠረት የመንግስት የልማት ድርጅት ሆኖ እንዲዋቀር አድርጓል።
ይህ ድርጅት ከተሰጡት ተልእኮዎች መካከል አንዱ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የኢንዱስትሪ ግብአቶችንና ውጤቶችን በማቅረብ፣ የግብአት አቅርቦትን ለማረጋገጥ የሚረዱ ፕሮጀክቶችን በማልማትና በማስተዳደር፣ በማስተላለፍ በተፈጥሮ ሃብትና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአሰራር ስርዓት በመተግበር ተወዳዳሪና ውጤታማ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እንዲፈጠር ድጋፍ ማድረግ ነው። የአቅም ውስንነቱ አሁን ያንን ለማከናወን የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ ለመፍጠር ባያስችለንም፤ድርጅቱ ግብአቶችን ገዝቶ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ራሱ ግብአቶችን በማልማት ኢንዱስትሪዎችን የመደገፍ ሚናም የተሰጠው ተቋም ነው። ኢንዱስትሪዎችን ተጠቃሚ ሲያደርግ፥ግብአት አቅራቢውንም አካል ጎን ለጎን ተጠቃሚ አድርጓል።
ድርጅቱ በዋናነት የሚያቀርባቸው የኢንዱስትሪ ግብአቶች የግብርና ውጤቶች ናቸው፡፡ በዚህም ግብርና መር ኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂውን ይደግፋል። እንደ ማሳያ ጥጥን ብንወስድ ከዚህ በፊት ምርቱ ዋጋው ሲወርድ አምራቹ አርሶ አደር በሚቀጥለው የምርት ወቅት ጥጡን አቁሞ ወደ ሩዝ ይሸጋገር ነበር። አሁን ድርጅቱ አርሶና አርብቶ አደሩ ያመረተውን ምርት የሚሸጥበት የማይነጥፍ ገበያ ስለፈጠረለት ሳያቋርጥ ማምረቱን ይቀጥላል። ግዥና ሽያጭ የምንፈጽመው ወቅታዊውን የዓለም አቀፍ ገበያ የምርት መሸጫና መግዣ ዋጋ ታሳቢ አድርገን ስለሆነ የሚያመርተው አካል በቀጥታ ተጠቃሚነቱ ከፍተኛ ይሆናል። ከፍተኛ ትሥሥርም ፈጥሯል። ቀደም ሲል አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የሚያመርተውን ጥጥ ለአቅራቢዎች ሲሸጥ በነበረበት ወቅት፣ምርቱ ወደ ኢንዱስትሪዎቹ በጥራትና በፍጥነት እንዳይደርስ ያደርግ የነበረው አሉታዊ ተጽእኖ ተቃሏል።
አዲስ ዘመን፡- ድርጅቱ በዋናነት የሚያቀር ባቸው የኢንዱስትሪ ግብአቶችን ይጥቀሱልኝ ?
አቶ መላኩ፡-የኢንዱስትሪ ግብአት ስንል መንግስት ቅድሚያ የሰጣቸው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ግብአቶች በመሆናቸው ቅድሚያ ከሰጣቸው ዘርፎች ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ሲሆን ለዘርፉ የሚሆኑ ግብአቶች በተለይ ጥጥ፣እንዲሁም ጥሬ ቆዳና ሌጦ፣ለኢንዱስትሪ ምርት የሚውል ጨው ይጠቀሳሉ። አሁን ዘግይተን ደግሞ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ፕሮሰሲንግ የሚያስፈልጉ ግብአቶችንም ማቅረብ ጀምረናል። በእነዚህ ብቻ ላለመታጠር ደግሞ ኬሚካልና አክሰሰሪዎችን (ተጓዳኝ እቃዎችን) ለማቅረብ ከሚመለከታቸው የዘርፍ መስሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት ጥናት አጥንተን ቅድመ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡-ድርጅቱ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለኢንዱስትሪ ግብአት ምን ያህል ወጪ አውጥቷል ? ምን ያህል የግብአቶች መጠንስ አቅርቧል ?
አቶ መላኩ፡- ድርጅቱ ከ 2007 እስከ 2009 ዓ.ም በጀት ዓመት ድረስ ወደ 899 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ግብአቶችን ለኢንዱስትሪዎች አቅርቧል። በ2010 በጀት ዓመት ያለፉት ሰባት ወራት ብቻ ወደ 258 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ዋጋ ያለው ግብአት ማቅረብ ችሏል። በአጠቃላይ ድርጅቱ ከተቋቋመ በኋላ አንድ ነጥብ 16 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ የኢንዱስትሪ ግብአቶች 22 ለሚሆኑ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ማቅረብ ችለናል።
አዲስ ዘመን፡-የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት የተቋቋመበት ካፒታል ምን ያህል ነበር ?
አቶ መላኩ፡-ድርጅታችን ሲቋቋም የተፈቀደለት ካፒታል 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ጅንአድ ውስጥ የነበረ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር አስቀድሞ ተከፍሏል። ቀሪው አልተከፈለም።
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ የኢንዱስትሪ ግብአቶችን ከየት እየገዛ ያቀርባል? ከአገር ውስጥ ወይስ ከውጭ ?
አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ግብአቶችን የምናቀርበው በዋነኛነት ከአገር ውስጥ ገዝተን ነው፤ነገር ግን በዚህ ብቻ አይታጠርም፥አገር ውስጥ የሌለ ግብአት ከሆነ ከውጭ የማንገዛበት ምንም ምክንያት የለም። ኬሚካሎችና አክሰሰሪዎች እና ሌሎች የኢንዱስትሪ ግብአቶችን ማቅረብ ስንጀምር ወደ ውጭ ገበያ እንገባለን።
አዲስ ዘመን፡-ድርጅቱ የኢንዱስትሪ ግብአት የሚያቀርበው ለሃገር ውስጥ ፋብሪካዎች ብቻ ነው?
አቶ መላኩ፡-ግብአቶችን ለኢንዱስትሪዎች ስናቀርብ በዋነኛነት የምናተኩረው የወጪ ንግድ መር የኢንዱስትሪ ልማት አቅጣጫውን የሚደግፉ አምርተው በወጪ ንግድ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ኢንዱስትሪዎችን ቅድሚያ እንሰጣለን። ስለዚህ የአገር ውስጥ የውጭ ባለሃብት ብለን ሳንለይ ለሁሉም ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ይህን ስንል አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን እንዘነጋቸዋለን ማለት አይደለም።ባሉን የመሸጫ ማእከላት እና ቅርንጫፎች ጥሬ ቆዳና ሌጦ እንዲሁም ከፊል ያለቀለት የቆዳ ውጤቶች እናቀርብላቸዋለን።
አዲስ ዘመን፡-ድርጅቱ በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ውጭ የላካቸው የኢንዱስትሪ ግብአቶች አሉ?
አቶ መላኩ፡- አሁን ተልእኳችን ግብአቶችን ወደ ውጭ መላክ አይደለም።በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በቂ ግብአት አግኝተው ችግራቸው ተቀርፏልም ማለት አይቻልም።ስለዚህ የኢንዱስትሪ ግብአት ወደ ውጭ አላክንም።
አዲስ ዘመን፡- የልማት ድርጅት እንደመሆኑ መጠን በዚህ ጊዜ ውስጥ ካቀረበው የኢንዱስትሪ ግብአት ምን ያህል ትርፍ አግኝቷል ?
አቶ መላኩ፡- ተቋሙ ትልቁ የተቋቋመበት ግብ ትርፍ ሳይሆን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን የግብአት ችግር ከመሠረቱ መፍታትና ዘርፉ በአለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያስችል ድጋፍ ለመሥጠት ነው። ተቋሙ የኢንዱስትሪውን ችግር ለማቃለል የተቋቋመ ተጠሪነቱ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሆነ የልማት ድርጅት ነው።
አዲስ ዘመን፡-ድርጅቱ የተሠጠውን ኃላፊነት እንዳይወጣ ያደረጉትና ትኩረት ሊሠጥባቸው የሚገባ ማነቆዎችን ቢያብራሩልኝ ?
አቶ መላኩ፡-በተወሰነ ደረጃ የኢንዱስትሪ ግብአት እጥረት ችግርን ማቃለል ችለናል። ነገር ግን፤አሁንም የኢንዱስትሪ ግብአት ችግር ሙሉ በሙሉ ተቃሏል ብለን አናስብም። ተቋማችን የተሰጠውን ተልእኮ በተሟላ ሁኔታ እንዳይፈፅም ካደረጉት ችግሮች ትልቁ ለድርጅቱ ማቋቋሚያ የተፈቀደው ካፒታል ባለመለቀቁ፣በሃብት ውስንነት የሚገደብ ተቋም አድርጎታል። እኛ የግብአት ግዢ አከናውነን ለኢንዱስትሪዎች በስድስት ወር የመመለሻ ጊዜ ተዋውለን በዱቤ ሽያጭ እናስተላልፋለን። አሁን ባለው አዝማሚያ አብዛኞቹ ኢንዱስትሪዎች በዱቤ ከወሰዱ በኋላ በውላችን መሠረት ክፍያ አይፈፅሙም። ይሄ በድርጅቱ አቅም ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል። የወሰዱትን በተባለው ባለመመለሳቸው ወደ ህግ እያቀረብናቸው ያሉ ድርጅቶችም አሉ፡፡ ሌላ ድርጅቱ አዲስ ተልእኮ የተሰጠው እንደመሆኑ መጠን ወደ ፊት ሊያራምድ የሚችል መዋቅራዊ አደረጃጀት ፈጥረናል። ነገር ግን ዘርፉ ብቁ ሙያተኛ የሚፈልግ ስለሆነ፤ የሰው ሃይል በሟሟላትና በማብቃትና ስትራቴጂ የማዘጋጀት ሂደት ላይ ነን።
አዲስ ዘመን፡- የድርጅቱን የማስፈጸም አቅምን እየተፈታተኑ ያሉት ችግሮች እንዲፈቱ እያደረጋችሁት ያለው ጥረት ምን ይመስላል ?
አቶ መላኩ፡- ያልተከፈለው የመቋቋሚያው ካፒታልን በተመለከተ ጥያቄያችንን ለመንግስት አቅርበን መፍትሔ እየጠበቅን ነው። ብድር ወስደው እዳቸውን በወቅቱ ባለመመለሳቸው ያጋጠሙን ችግሮችን ከባለሃብቶችና ባለሃብቶቹን በቀጥታ ከሚደግፉ የዘርፍ መስሪያ ቤቶች ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረግን ነው። የሰው ሃይል ችግርን ለመፍታትም ይህንን ተልእኮ ሊሸከም የሚችል አዲስ አደረጃጀት ነው የሰራነው። አደረጃጀት መሥራት በራሱ ግብ ስለማይሆን ዘርፉን የሚስፈልገውን ሙያተኛ ይዘን ለመንቀሳቀስ አዳዲስ የሙያ ስብጥሮችም አካተናል።

በሪሁ ብርሃነ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።