ቀጣይነትን የሚጠይቀው የከተማ ሴፍቲኔት

14 May 2018

ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ለምግብ እጦት ይዳረጋሉ፡፡ የምግብ እጦት ደግሞ አንድም ጊዜያዊ ሆኖ፤ ካልሆነም ስር የሰደደ ሆኖ ሊከሰት ይችላል፡፡ ስር የሰደደ ሲባል የቤተሰቡ ጥሪት በጣም የተመናመነና ከድህነት ወለል ሲገኝ ነው፡፡ በአንፃሩ ጊዜያዊ ችግር ደግሞ በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሰራሽ አደጋ ምክንያት በሚደርሱ ችግሮች የሚፈጠር የምግብ እጦት ነው፡፡
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት የማህበራዊ ነክ ዓላማዎች በሚዘረዝረው _አንቀጽ 90 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ እንደተመላከተው፤ _የአገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የትምህርት፣ የጤና አገልግሎት፣ የንፁህ ውሃ፣ የመኖሪያ፣ የምግብና የማኅበራዊ ዋስትና ሊኖረው እንደሚገባ በግልጽ ደንግጓል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 41 ንዑስ አንቀጽ 5 መሠረት መንግሥት የአካልና የአዕምሮ ጉዳተኞችን፣ አረጋውያንንና ያለ ወላጅ ወይም ያለ አሳዳጊ የቀሩ ሕፃናትን ለማቋቋምና ለመርዳት የአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደው ደረጃ እንክብካቤ እንደሚያደርግ አስቀምጧል፡፡ በንዑስ አንቀጽ 6 ለሥራ አጦችና ችግረኞች ሥራ ለመፍጠር የሚያስችል ፖሊሲ በመቅረፅ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶችን ማካሄድ፣ በንዑስ አንቀጽ 7 ለዜጎች የሥራ ዕድሎች እንዲስፋፉ መንግሥት አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባው አስፍሯል፡፡
በተመሳሳይ በአንቀጽ 43 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይም የመንግስት የልማት እንቅስቃሴ ዓላማ የዜጎችን ዕድገትና መሠረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት እንደሆነም ያስቀምጣል፡፡ በጥቅሉ የሕገ መንግሥቱ በኢኮኖሚ ልማት መሠረታዊ ትኩረቱ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዋስትና ማረጋገጥ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን፣ ከዚህ አንፃር የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጉዳይ ሕገ መንግሥታችን ከአቅም ጋር እየተገናዘበ መሟላት ያለበት መብት መሆኑን በግልጽ አስፍሯል፡፡ ይሄን መነሻ በማድረግ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የምግብ ዋስትና ስትራቴጂ የሰው ልጅ የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት የአጭር ጊዜ የምግብ አቅርቦት ችግርን በማቃለል ዜጎችን በቀጣይ ከከፋ ድህነትና ከተመጣጠነ ምግብ ዕጦት ችግር በራሳቸው ጥረት ደረጃ በደረጃ በማላቀቅ፣ ዘላቂነት ባለው መንገድ እንዲቋቋሙና የተሻለ ኑሮን እንዲመሩ የተመቻቸ ሁኔታ የሚፈጥር ነው፡፡
የምግብ ዋስትና ስትራቴጂው ዝቅተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸውንና የመሥራት አቅም ያላቸው ዜጎች ከኅብረተሰቡ ጋር ሆኖ በጥንቃቄ_ በመለየት ጉልበት፣ ሀብት፣ ክህሎትና ዕውቀታቸውን አቀናጅተው ኑሮአቸውን በዘላቂነት ለመምራት የሚያግዙ እሴትን የሚጨምሩ የአካባቢ ልማት ሥራዎችን በስፋት መሥራት ነው፡፡ በቀጣይም ኑሮአችውን ሊመሩበት የሚያስችላቸውን ጥሪት በማፍራት መቆጠብ የሚያስችልና በተደራራቢ የአካል ጉዳት፣ በዕድሜ፣ በጤና፣ ወዘተ ምክንያት በሥራ ላይ መሰማራት ለማይችሉ ዜጎች የቀጥታ ድጋፍ የሚሰጥበትም ነው፡፡ ይህም በመንግሥት፣ በልማት አጋሮችና በኅብረተሰቡ ጥምር ተሳትፎ የሚተገበር ነው፡፡
የምግብ ዋስትና ስትራቴጂ እያንዳንዱ ዜጋ መጠንና ጥራትን ባማከለ መልኩ እንዲሁም ባልተቆራረጠ መንገድ ምግብ ዋስትናው ሊረጋገጥለት እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡ በአንፃሩ ከተሞች ያላቸውንም ዕምቅ ሀብት ባለመጠቀማ ቸውና በአብዛኛው ሊባል በሚችል ደረጃ ከገጠር በሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ላይ ጥገኛ በመሆናቸው፣ የምግብ ዋስትና ችግሮችን በመሠረታ ዊነት ማቃለል አልቻሉም፡፡ በከተሞች በተለያዩ አካላት እየተካሄዱ ያሉ በመንግሥት የሚቀርቡ መሠረታዊ ሸቀጦችና ሌሎች የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሥራዎችም ለደሃ ተብለው የተቀረፁ ቢሆኑም፣ በአፈጻጸም ረገድ ግን ለታለመለት ማኅበራዊ ሥራ የማይደርሱ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሥራዎቹ ያልተቀናጁና ያልተናበቡ በመሆናቸው፣ የሀብት ብክነትና የጥገኝነት ስሜት ከማስፈናቸውም በላይ፣ ዘላቂ ውጤት ማምጣት ላይ ክፍተት ይስተዋልባቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎችንና ልዩ ድጋፍ የሚያስፈል ጋቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ሴተኛ አዳሪዎች እንዲሁም አቅመ ደካሞችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መንግስት ፕሮጀክት ቀርፆ ወደ ተግባር ከገባ አንድ አመት ሆኖታል፡፡ በዚህ አመት ውስጥ በአዲስ አበባ፣ በሀዋሳ፣ በመቀሌ፣ በአዳማ፣ በድሬዳዋ፣ በጅግጅጋና በደሴ እንዲሁም በሌሎች አራት ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎችን በስራ እንዲሰማሩ በማድረግና በቀጥታ ድጋፍ በመስጠት ውጤታማ ስራ ተሰርቷል፡፡
የስራ እንቅስቃሴውን አስመልክቶ የከተማና ቤቶች ልማት ሚኒስቴር ከፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት ጋር በመተባበር ሰሞኑን ውይይት ተደርጓል፡፡ በውይይቱም በከተሞች ምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ስራው ላይ የነበሩ ውጤቶች፣ ችግሮችና በቀጣይ የሚፈቱበት መንገድ ተነስቷል፡፡ በወቅቱም የፌዴራል የከተሞች የምግብ ዋስትና እና የስራ እድል ፈጠራ ኤጀንሲ ተቀዳሚ ምክትል ዋና ዳሬክተር አቶ ሰለሞን አሰፋ እንደተናገሩት፤ በከተሞች ላይ የሚገኙ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ በአስራ አንድ ከተሞች ላይ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ስራ ተጀምሯል፡፡
አቶ ሰለሞን፣ በከተሞቹ ላይ በስራ ታታሪነት መጓደል፣ የልማታዊ መልካም አስተዳደር ችግር፣ የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት አለመኖር እንዲሁም ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ መንስኤ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ለመርሃ ግብሩ ትግበራ በተመረጡት በአስራ አንዱም ከተሞች ባለፈው ዓመት ስራው እንደተጀመረና በአዳማ፣ በሀዋሳ፣ ጅግጅጋ፣ መቀሌ፣ ደሴ እንዲሁም ድሬዳዋ ውጤታማ ስራ መሰራቱን ያመለክታሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከሚገኙ 116 ወረዳዎች ውስጥ በመጀመሪያው ዙር 55 ወረዳዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተይዞ ወደ ስራ ቢገባም በስምንት ወረዳዎች ላይ ውጤታማ ስራ አለመሰራቱን ይገልፃሉ፡፡ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በአረንጓዴ ልማት፣ በደረቅ ቆሻሻና በአካባቢ ልማት ስራዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ገንዘብ እየተከፈላቸው እንደሚገኝ ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፤ ምንም እንኳን መርሃ ግብሩ በዚህ መልኩ ጥሩ ውጤት እያመጣ ቢሆንም በስራው ላይ የቀጥታ ተረጂዎች ክፍያ ማነስ፣ ለአካባቢ ልማት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች በጊዜው አለመሟላት እንዲሁም በሚሰሩ የልማት ስራዎች ላይ የሚመለከታቸው ክፍሎች የቅንጅት ጉድለት ተስተውሏል፡፡ ከዚህ አኳያ በልዩ ድጋፍ ስር የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ሴተኛ አዳሪዎችና ለምኖ አዳሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተይዟል፡፡ ሆኖም ስራው በጥናት የተደገፈ መሆን ስላለበት በተያዘው በጀት አመት መጨረሻ ወደ ተግባር ይገባል፡፡
ከአዲስ አበባ የስራ እድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የመጡት አቶ ዘሩ በለጠ በበኩላቸው፤ በመርሃ ግብሩ በከተማው በተመረጡ ወረዳዎች ላይ 55 ወረዳዎች ላይ ከድህነት በታች የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ስራዎች ቢጀመሩም በስምንት ወረዳዎች ላይ ዝቅተኛ ውጤት መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ በተቀሩት 47 ወረዳዎች ላይ ግን ውጤታማ ስራ መሰራቱንም ይጠቅሳሉ፡፡
በተፋሰስና በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስራዎች ላይ በጉለሌ፣ በየካና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ላይ ለውጥ ያመጣ ስራ መሰራቱን የሚጠቁሙት አቶ ዘሩ፤ በቀጥታ ድጋፍ ለሚደረግላቸው ዜጎችም በወቅቱ ክፍያ እንደሚከናወንላቸውም ያመለክታሉ፡፡ በስራ እንቅስቀሴው ላይ በዋናነት በአካባቢ ልማት ስራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች የልጆች ማቆያዎች አለመኖር እንደ ችግር ያነሳሉ፡፡
የሀዋሳ ከተማ የከተሞች የምግብ ዋስትና እና የስራ እድል ፈጠራ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ መልካሙ ሀይሌ እንደሚሉት፤ በከተማው በአንድ ዓመት ውስጥ ቀጥታ ድጋፍ ለሚደረግላቸው ዜጎች 36 ሚሊዮን ብር እንዲከፈል ተደርጓል፡፡ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ ቀሪ ስራዎችን የሚጠይቅ ሲሆን፤ በዚህም በቀጣይ 11 ሺ ዜጎችን በአምስት ቀበሌና በሁለት ክፍለ ከተሞች ተጠቃሚ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡
አቶ መልካሙ፣ በዓመቱ ውስጥ ካጋጠሙ ችግሮች መካከል ተጠቃሚዎቹ የባንክ አካውንታቸው ሲጠፋ በምትኩ የሚሰጣቸው አዲስ ቁጥር በመሆኑ ለማስተናገድ መቸገራቸውን ይጠቁማሉ፡፡ በከተማው ላይ የሚገኙ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግም ስራዎች ቢጀመሩም ወደ ሌሎች ከተሞች በተደጋጋሚ ያለው ፍልሰት እክል መፍጠሩን ይጠቅሳሉ፡፡
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ሂሩት ቢራሶ፤ በከተሞች ላይ የህብረተሰቡን ድህነት ለመቀነስና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝና በዚህም 450 ሚሊዮን ዶላር በእርዳታና በመንግስት ድጋፍ በጀት ተይዞ ስራዎች መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡ በዚህም አራት ሚሊዮን ሰባት መቶ ሺ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተይዞ በአንድ አመት ውስጥ በአካባቢ ስራዎችና በቀጥተኛ ድጋፍ ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡
በምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ስራው ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች ከጥገኝነትና ከጠባቂነት እንዲወጡ ለማስቻል ቀጣይነት ያለው የስራ ፈጠራ ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግ እቅድ መያዙን ይጠቅሳሉ፡፡ በአስራ አንድ ከተሞች የሚገኙ ከድህነት በታች የሚገኙ ዜጎች በአረንጓዴ ልማት፣ በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ እንዲሁም በተፋሰስ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ገቢ እያገኙ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

መርድ ክፍሉ 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።