ማህበራትና የሂሳብ ኦዲትን ለማቀራረብ Featured

15 May 2018

የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ በገጠርና በከተማ የሚኖረውን ህብረተሰብ የአካባቢውን ሀብት መሰረት በማድረግ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሩን ለመፍታት በፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ በተለያዩ አይነትና ደረጃ የህብረት ስራ ማህበራትን ያደራጃል፤ አቅማቸውንም ይገነባል። የገበያ ድርሻቸውን በማሳደግ እንዲሁም በህግና ደንብ እንዲመሩ በማድረግ የአባላቱን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የህብረት ስራ ማህበራትን የመፍጠር ተግባርም ይከውናል።
ኤጀንሲው ይህን ተልዕኮ በማንገብ ባለፉት ዓመታት ባከናቸው ተግባራትም መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ በአሁን ወቅት በአገሪቱ ከ18 ሚሊዮን በላይ አባላትን ያፈሩ ከ84 ሺ በላይ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት፤ 384 የህብረት ስራ ዩኒየኖች እንዲሁም ሶስት የህብረት ስራ ፌዴሬሽኖች በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ይገኛሉ።
በአጠቃላይም ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማፍራት የቻሉት የእነዚህ ማህበራት፣ ዩኒየኖችና የህብረት ስራ ፌዴሬሽኖች የ2010 ዓ.ም የዘጠኝ ወር እቅድ አፈፃፀምም በቅርቡ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ተካሂዷል።
«የህብረት ስራ ማህበራትን በማጠናከር የህዝቦችን የልማት ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን» በሚል መሪ ሐሳብ የተካሄደውን የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርትና ግምገማ በመመልከት መረዳት እንደተቻለው፤ ኤጀንሲው ባለፉት ዘጠኝ ወራት የህብረት ስራ ማህበራት በማጠናከር፣ የግብይት ድርሻቸውን በማስፋት፣ የማህበራት ቁጠባና ኢንቨስትመንትን በማጎልበት ረገድ ምንም እንኳን ከክልል ክልል አፈፃፀሙ ልዩነት ቢኖረውም ውጤታማ የሚባሉ ተግባራት ማከናወን ችሏል። ይሁንና የኤጀንሲው የትኩረት መስኮች አንዱ በሆነው የህብረት ስራ ማህበራት ህጋዊነትና ደህንነት በማረጋገጥ ረገድ ህግን አክብረው የሚሰሩ ጤናማ የህብረት ስራ ማህበራትን የመፍጠር ተግባር አሁንም ትኩረት የሚፈልጉ ቀሪ ስራዎች እንዳሉበት ተመላክቷል።
አዲስ ዘመንም ይህን ዋቢ በማድረግ ለመሆኑ ህብረት ስራ ማህበራት በተለይ በኦዲትና ኢንስፔክሽን ረገድ የሚስተዋሉባቸውን ችግሮች ለዓመታት መሻገር ያቃታቸው ስለምን ይሆን? ወይስ ለውጦች መታየት ጀምረዋል? ሲል ጥያቄ አንስቷል።
በዚህ ረገድ ለሚነሱ ጥያቄዎች የኦሮሚያ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳኛቸው ሽፈራው፤ ህብረት ስራ ማህበራት በርካታ ገንዘብ የሚቀንሳቀስበት እንደመሆኑም የማህበራት ትልቁ ስጋትና ማነቆ ኪራይ ሰብሳቢነት መሆኑን ይገልፃሉ። «ኦሮሚያ ብንወስድ በማህበራት ዘንድ በአጠቃላይ 18 ቢሊዮን ብር ይንቀሳቀሳል፤ይህን ያህን ገንዘብ በሚንቀሳቀስበት ዘርፍ ደግሞ ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ የግድ ይላል፡፡ ሆኖም ጠንካራ ቁጥጥር በማድረግ ረገድ ክፍተቶች አሉ፡፡ በተለይ የሂሳብ ስራ የግድ በባለሙያ የሚሰራ ቢሆንም፤ ማህበራት ስራቸውን የሚሰሩበት በብቁ ባለሙያ ታግዘው አይደለም፡፡ ይህም የብቁ የባለሙያ እጦትም ጠንከር ያለ የፋይናንስ ስርዓት መተግበርን አዳጋች አድርጎታል» ይላሉ።
ክልሉ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ህግን አክብረው የሚሰሩ ጠንካራ የህብረት ስራ ማህበራትን ለማጎልበት በተለይ የሂሳብ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ስራዎችን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የሚገልፁት አቶ ዳኛቸው፤ በዚህ ዓመት የአሰራር፣ የአመለካከት እንዲሁም የአቅም ክፍተቶቹን የመለየት ስራ አጠናክሮ መስራቱን ያስረዳሉ።
በዚህ መሰረት ዋና ዋና የተባሉ ማህበራትና ዩኒየኖች ላይ ጠንካራ የቁጥጥር ስራ መሰራቱንና 17 የሚሆኑ ሞዴል ደንብና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ስልጠና መሰጠቱን የሚገልፁት አቶ ዳኛቸው፤ በዚህም ምክንያት ምንም እንኳን ችግሩ በአንድ ጀንበር የሚፈታና ሰፊ ትግል የሚጠይቅ ቢሆንም፤ ቀደም ባሉት ዓመታት በማህበራት አካባቢ የሚስተዋሉ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካክትና ተግባራት እየቀነሱ መምጣታቸውን ነው የተናገሩት።
ለአብነት ተመዝብረው የነበሩ ንብረቶችን ከማስመለስ ረገድ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 36 ሚሊዮን ብር ማስመለስ ተችሏል፤ ‹‹የህዝብ ገንዘብ ያጎደሉ ግለሰቦችም በአደባባይ እንዲታወቁ የማድረግ ተግባር ተከውኗል» የሚሉት አቶ ዳኛቸው፤ ይሁንና መሰል ተግባራት በሚከወኑበት ወቅት ማነቆ የሚሆኑና በክፍተቶቹ ተጠቃሚ የሆኑ አካላት በመኖራቸው የእነዚህን ግለሰቦች እንቅስቃሴ ማጥራትም የግድ ነው ባይ ናቸው።
የአማራ ክልል የህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የህብረት ስራ ማህበራት ማደራጃ ዳይሬክተር አቶ አለምዘውድ ስሜነህ እንደሚገልፁት ከሆነም፤ ህብረት ስራ ማህበራት ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶቻቸው ባሻገር በአንድም ሆነ በሌላ መልክ የሚታወቁት የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ተያይዞም ጭምር ነው። መሰል ተግባርና አመለካከትን ማስወገድና ህጋዊና ህጋዊነትን ማስጠበቅ የሚቻለው ደግሞ ማህበራት ምን ያህል ሃብት አላቸው፤ የፋይናንስ እንቅስቃሴያቸው ምን ይመስላል? የሚሉትን ጨምሮ አጠቃላይ ቁመናቸው በአግባቡ ተመርምሮ ሲታወቅ ነው።
እንደ አቶ ዓለምዘውድ ገለፃ፤ ህግና ህጋዊነትን በመከተል ረገድ ህብረት ስራ ማህበራት መተዳደሪያ ደንባቸው ላይ በተቀመጠው አግባብ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ኦዲት መደረግ አለባቸው። ይሁንና ይህን ለማድረግ በተለይ በኦዲት ሪፖርት ረገድ አቅም ያላቸው ሂሳብ ሰራተኞች ባለመኖራቸው ማህበራት ሂሳብን በወቅቱ የማሳወቅ፤ በወቅቱ ካሳወቁም በአግባቡና በተደራጀ መልኩ ለኦዲተሮች ያለማቅረብ ችግር አለባቸው። ይህም ኦዲተሮች ሂሳቦችን ለማስተካከል ረጅም ጊዜ እንዲወስድባቸውና የኦዲት ስርዓት መቶ በመቶ ህግና ህጋዊነትን ጥብቆ እንዳይከናወን እክል ፈጥሯል።
ማህበራት በዓመት አንድ ጊዜ ኦዲት ከመደረጋቸው በተጓዳኝ፤ የተገኙ የኦዲትና የኢንስፔክሽን አስተያየቶች ተደራጅተው ስድስት ወር ውስጥ ለአደራጅ አካል መቅረብ እንዳለባቸው በህገ ደንብ መቀመጡን የሚያስረዱት አቶ ዓለም ዘውድ፤ ይሁንና ግኝቶችንም ሆነ የኦዲት አስተያየቶችን መሰረት በማድረግ አደራጅ አካል ተከታትሎና አርሞ ዳግም ችግሮቹን ማስወገድ በሚያስችል ረገድ ክትትልና ድጋፍ የመስጠት ውስንነት እንዳለበትና ግኝቶችም ካሉበት መደርደሪያ ላይ ከመቀመጥ ባሻገር አለመውረዳ ቸውን ነው የሚገልፁት።
ክልሉም በኢንስፔክሽን ስራዎች ረገድም ህብረት ስራ ማህበራትን ከአሰራር፣ ከአመራርና አደረጃጀት አንፃር ያላቸው እንቅስቃሴ ጥፋት ያጠፉ ሰዎች በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ተግባር መጀመሩን ነው ያብራሩት።
የአፋር ክልል የህብረት ስራ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ነኢማ መሀመድ ማህበራት ህግና ህጋዊነት ጠብቀው እንዲሰሩ በማድረግ ረገድ እንደ ክልል ብዙ አለመሰራቱንና ማህበራትም ህግና ደንቡን የተከተለ የሂሳብ አያያዝ ስርዓቶችን በመከተል ረገድ ችግር እንዳለባቸው አልሸሸጉም።
ወይዘሮ ነኢማ፣ የችግሩ ዋነኛ ምክንያት ብለው እንደሚገልፁትም፤ የባለሙያ እጦት እንዲሁም የአቅም ውስንነት ቀዳሚ ሲሆኑ፣ የንብረት፣ የምዝገባና ኮድ አለመሟላትም ሌላኛው ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ። ይህ ባለመሟላቱም ኦዲተሮች ስራቸውን በአግባቡ መስራት አለመቻላቸውን ያመለክታሉ። መሰል ክፍተቶች በማስወገድና የማህበራት ሁለንተናዊ ሚና ለማጎልባት የህብረት ስራ ፅህፈት ቤት እንደ ክልል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና ክልሉ የባለሙያዎች እገዛ ሊደረግለት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑስማን ሱሩር፤ ‹‹የህብረት ስራ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ላይ በፈለግነው ልክ ስኬታማ እየሆንን አይደለም፤ የኦዲት ሽፋንን ማሳደግና ጉድለቶችን ማስቅረትም የህብረት ስራ ማህበራት ዋነኛ ችግር ነው›› ይላሉ።
እንደ አቶ ኡስማን ገልፃ፤ የህብረት ስራ ማህበራት ለአባሎቻቸው ግልፅነት በመፍጠር፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በአግባቡ ምላሽ በመስጠት ረገድ አሁንም ያልመለሳቸው ጥያቄዎች አሉ። በተለይ ዞንና ወረዳዎች ላይ በቂ ባለሙያ የለም፤ በቂ ሀብትም አይመደብም። እንዲሁም በቂ የአበልና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች አይሟሉላቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት ባለሙያዎች ለመስራት ፈቃደኛ አይሆኑም። ይህም አመራሩ ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት በቂ አለመሆን ውጤት ነው። ጉዳይ የመልካም አስተዳደር ችግርን የመፍታት በመሆኑ አመራሩ ይህን በማሰብ ይበልጥ መስራት አለበት ነው የሚሉት፡፡
ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች እንደሚናገሩት፤ የህብረት ስራ ማህበራት ከአባላት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ብሎም ለአገር ሁለንተናዊ እድገትና በተለይ ድህነትን በመቀነስ ረገድ ያላቸውን ተልዕኮ እጅጉን ትልቅ ነው። ይሁንና ይህን የማህበራት አገራዊ ተልዕኮና ሚና ከመንግሥት ጀምሮ ሁሉም አመራር በአግባቡ ያለመገንዘብ ችግር በስፋት ይስተዋላል። ለህብረት ስራ ማህበራት ትልቅ ትኩረት በመስጠት በቂ በጀት ከመመደብና ህብረት ስራ ማህበራት የሚያቀርቡትን ችግሮች በቅርበትና በፍጥነት ከመፍታት አንፃር ጠንካራና ታማኝ የሆነ አመራርን በመመደቡ ረገድ ውስንነቶች አሉ።
ሆኖም የህብረት ስራ ማህበራት አገራዊ የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ለማሳደግ በተለይ በህብረት ስራ ማህበራት አካባቢ የሚስተዋለው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርን ለማስወገድ ከተፈለገ በቀጣይ መሰል ክንውኖች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራባቸው የግድ ይላል።

ታምራት ተስፋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።