ባዮ ቴክኖሎጂና ሰው ሰራሽ አስተውሎት -የመጪው ዘመን መወዳደሪያዎች

16 May 2018

እኤአ በ2017 ጥቅምት ወር ላይ የዓለምን ቀልብ የሳበ፣ አግራሞትን የፈጠረ፣ ድንቅ የቴክኖሎጂ ውጤት መሆኗ የተነገረላት ሶፊያ የተባለች ሮቦት ይፋ ሆነች፡፡ ሶፍያ እንደ ሰው ታወራለች፣ ጥያቄዎችን ትመልሳለች፣ ትተነብያለች፤ በቃ ሰው ሰራሽ ሰው ሆና ብቅ ብላለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ድንቅ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤት ሆና ተመዝግባለች፡፡ በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ የሳዑዲ ዐረቢያ ዜግነት ያገኘች ሮቦት ስትሆን፤ የሰውን ህይወት የተሻለ ለማድረግ በሚደረጉ ስራዎች በመሳተፍ ውጤት የማምጣት ሀሳቧ እንዳላት ተናገራለች፡፡
ዛሬ የዓለም ቴክኖሎጂ እዚህ ላይ ደርሷል፡፡ ነገ የት እንደሚደርስ መገመት አያዳግትም፡፡ ቴክኖሎጂ የኢኮኖሚ አቅም ማፈርጠሚያ በሆነበት ዘመን ቴክኖሎጂን ለመፍጠር ስርዓት መዘርጋትና ተቋም መፈጠር ቅንጦት አይሆንም፡፡ ምክንያቱም የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች በግለሰብም ሆነ በተቋማት ደረጃ ይፈልቃሉና። የእነዚህ ምርምር ውጤቶች የሚለኩት ደግሞ ወደ ተግባር ተተርጉመው የህብረተሰቡን ህይወት ማሻሻል ሲችሉ ነው።
እናም በምርምርና በፈጠራ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ችግር የመፍታት አቅማቸው የሚፈተሸውም ለህብረተሰቡ ኑሮ መለወጥና ለአገር ዕድገት በሚያስገኙት ፈርጀ ብዙ ጥቅሞች ይሆናል። ስነ ህይወታዊ (ባዮቴክኖሎጂ) ሳይንስ እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቲፌሻል ኢንተለጀንስ) ወደ ተግባር ተተርጉመው ፈርጀ ብዙ ጥቅም እንዳስገኙ የበለፀጉ አገራት ተሞክሮ ያሳያል።
እነዚህ ቴክኖሎጂዎች የኢንዱስትሪና የግብርና ምርታማነትን በመጨመር፣ ጥራትን በማስጠበቅና ወጪን በመቆጠብ ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ እድገትና ለህዝብ ኑሮ መሻሻል የማይተካ ሚና እንዳላቸው የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።
በተለይ ከግብርናው ጋር አያይዘን ብናያቸው በፍጥነት የሚያድጉ፣ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ፣ በሽታንና ተባይን የሚቋቋሙ ጣፋጭ ፍራፍሬ ያላቸውን እፅዋቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ በማባዛት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ለማምረት የማይተካ ሚና አላቸው። እንዲሁም የግብርና ምርቶችን በጥሬ ዕቃነት የሚጠቀሙ ፋብሪካዎችንና የህዝቡን የምግብ አቅርቦት ፍላጎት ለማሟላት ወሳኝ ድርሻ ይኖራቸዋል። አዲሱን የባዮ ቴክኖሎጂ ሳይንስን ተጠቅሞ ምርታማነትን ማሳደግና ጥራት ያለው ምርት ማምረት በዓለም አቀፍ ገበያ የሚኖረውን ተወዳዳሪነት ያሳድጋል፡፡
‹‹በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርታማና በሽታን መቋቋም የሚችሉ አዋጭ አዳዲስ ዝርያዎችን በማባዛትና በማላመድ ምርታማነትን ለማሳደግ፤ እንዲሁም አገሪቱ ያላትን የብዝሀ ህይወት ሀብት ለማወቅና ለመጠቀም የሚስያችል አቅም ይፈጥራል›› የሚሉት የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዮት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ ናቸው፡፡
ዘመናዊው የባዮ-ቴክኖሎጂ ዘዴዎች ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ህብረ-ሕዋስን ማባዛት(ቲሹ ካልቸር) ቴክኖሎጂ አንዱ ነው። ይህ ዘዴ የዕፅዋትን ነጠላ ሕዋስ በመውሰድ በቤተ-ሙከራ በተቀመመ የንጥረ ነገር ውህድ ውስጥ እንዲራባ በማድረግ የዕጽዋት ችግኞችን የማበዣ ዘዴ ነው። ቲሹ ካልቸር በተለይ ከበሽታ ነጻ የሆኑ ወይም ብዛት ያለው ምርት የሚሰጡ እፅዋቶችን በአጭር ጊዜና በከፍተኛ መጠን ማምረት የሚያስችል ዘዴ እንደሆነ ነው ዶክተር ካሳሁን የሚገልፁት።
ቡናን በቲሹ ካልቸር ዘዴ በአጭር ጊዜ በማባዛት ምርታማና ጥራቱን የጠበቀ ማድረግ እንደሚቻል ዋና ዳይሬክተሩ ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ቡናን በቲሹ ካልቸር ዘዴ በማባዛት ምርቱን ለመጨመርና ጥራቱን ለማስጠበቅ በተበጣጠሰ መልኩ ጥረቶች ቢደረጉም ጠብ የሚል ውጤት ሊገኝ አልቻለም ፡፡ መንግስት የቴክኖሎጂውን አስፈላጊነት በመረዳት የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን ከአንድ ዓመት በፊት አቋቁሟል፡፡ኢንስቲትዩቱም እስካሁን በተናጠል ሲካሄዱ የነበሩትን ቡናን በቲሹ ካልቸር የማባዛት ስራ በተቀናጀና ውጤት በሚያመጣ መልኩ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የግብርና ማነቆዎችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው፡፡ በተመሳሳይ በምርት ሂደትና ክምችት ወቅት የሚከሰተውን አፍላ ቶክሲን የተባለውን ሻጋታ ኬሚካል (ፈንገስ) መከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለመፍጠር ፕሮጀክት ተቀርጾ የምርምር ስራ መጀመሩ ተነግሯል፡፡
ዶክተር ካሳሁን በአገር ደረጃ በአሀዝ የተደገፈ መረጃ ባይኖርም በፈንገስ የተጠቃን እህል መመገብ በሰው ጤና ላይ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ስለሆነም ምርቱን ገበያ አውጥቶ መሸጥ አይቻልም፡፡ለእንስሳት መኖ ቢውልም እንኳ ይህን የተመገቡ እንስሳት በስጋውም ሆነ በወተቱ አማካኝነት ፈንገሱ ወደ ሰው ተሸጋግሮ የጤና እክል ይፈጥራል ፡፡ለዚህ አሳሳቢ ችግር መፍትሄ የሚሰጥ ቴክኖሎጂ ለመፍጠርም እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በአፍሪካ ደረጃ ናይጄሪያ ፣ታንዛኒያና ኬንያ ቴክኖሎጂውን በምርምር አግኝተው ወደ ትግበራ መሸጋገራቸውን ዶክተር ካሳሁን ገልፀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ግን በችግሩ ዙሪያ በቂ መረጃ ባለመኖሩ ወደ ስራ ሳይገባ ተቆይቷል፡፡ ስለዚህ የጉዳቱ መጠንና እንዴት ሊፈጠር እንደሚችል በጥናት ከተለየ በኋላ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በመውሰድ ቴክኖሎጂውን ወደ ማመንጨት ስራ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለ10 ዓመት የምትመራበት የባዮ ቴክኖሎጂ መራሄ ድርጊት ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
‹‹ኢንስቲትዩቱ የታለመለትን ዓላማ ለማሳካት እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ ለስራው መሰረታዊ የሆኑ ቤተ ሙከራዎችን በማደራጀት ላይ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ የቤተ ሙከራ ዕቃዎችን የገዛ ሲሆን፤ ዘንድሮም ግዥ ለመፈፀም በጨረታ ሂደት ላይ ይገኛል›› የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ ይህ እስኪሟላ ድረስ የዩኒቨርሲቲዎችን ቤተ ሙከራዎች በመጠቀም ምርምርና ቴክኖሎጂ የማፍለቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ በሳይንስ ትምህርቶች የሰለጠነ የሰው ሀይል ቢኖርም የጥራት ጉዳይ አሳሳቢ ችግር ሆኗል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በውጭ አገራት ‹‹በትረ ሳይንስ›› የሚል ነጻ የትምህርት ዕድል መርሀ ግብር አዘጋጅተዋል፡፡ በዚህም ከአንድ ሺ በላይ ተማሪዎች በህንድ፣በቱርክና በቻይና በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ ይህም በቀጣይ ዕውቀትን መሰረት ያደረገ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስችላል፡፡
ባዩ ቴክኖሎጂና ሰው ሰራሽ አስተውሎት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን ያስችላል፡፡ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አይሲቲ ለልማት የምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋ ተገኝ ይህን በምሳሌ ያስረዳሉ፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል አንድ የታወቀና በሙያው የተካነ ዶክተር ቢኖር፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ዕውቀቱን አገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ ዶክተሮች በቀላሉ ማስተላለፍ ይቻላል፡፡ ይህም የህዝቡን የህክምና ወጪ ከመቀነስ ባለፈ ጤናው እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡
ሰው ሰራሽ አስተውሎት በዓለም ላይ ትልቅ ለውጥ እያመጣ እንደሆነ ዶክተር ተስፋ ይናገራሉ፡፡ ቴክኖሎጂው ለአገራቱ ገቢ ከማስገኝቱ ባለፈ ከኢኮኖሚ ዕድገታቸውም 20 መቶ ድርሻ አለው፡፡ በግብርና ዘርፍም የምርት ጥራትና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ተጨባጭ ውጤት ማሳየቱን ጠቅሰዋል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያም ለባዮቴክኖሎጂና ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ትኩረት በመስጠት እና ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የህብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታት የሚረዳ መሰረት ለመጣል የተቀናጀ ስራ ይጠይቃል ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳንሉካን ደበበ በበኩላቸው ቴክኖሎጂዎቹ የመጪው ዘመን መወዳደሪያ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ መንግስትም ይህን ታሳቢ በማድረግ በረጅም ዕይታ ኢንስቲትዩትን ማቋቋሙን ያስረዳሉ፡፡
‹‹ሁል ጊዜ ቴክኖሎጂዎችን ምዕራባዊያን ተጠቅመውበት ሲጨርሱት እኛ ጀማሪና ተከታይ መሆን የለብንም፡፡ ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ በመግዛትና በመቀበል በዓለም ተወዳዳሪ መሆን አዳጋች ነው፡፡ ቴክኖሎጂዎቹ የነገው ዘመን መወዳደሪያ በመሆናቸው ዛሬ መጀመር እንደሚገባ በማመን መስራት ይኖርብናል›› በማለት ከወዲሁ ቴክኖሎጂዎችን ለማመንጨት መሰረት መጣል እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
ሰው ሰራሽ አስተውሎት የማይገባበት ዘርፍ እንደሌለ አቶ ሳንሉካን ያስረዳሉ፡፡ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤት የሆነችው ሶፊያ ሮቦት ሲያናግሯት ትመልሳለች፡፡ ለምሳሌ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የት እንደሆነ ለሚጠይቃት፤ ዩኒቨርሲቲው የሚገኝበትን ቦታና ርቀቱን በኪሎ ሜትር ትናገራለች፡፡ የፌስ ቡክና የጎግል ብዙ ስርዓታቸው ከሰው ሰራሽ አስተውሎት መወሰዳቸውን አቶ ሳንሉካን ጠቁመዋል፡፡ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ኢኮኖሚን ከመደገፍና ከማቀላጠፍ ባሻገር የገቢ ምንጭም ናቸው፡፡
በኢንስቲትዩቱ የኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ማዕከል የአርቲፌሻል ቴክኖሎጂ ዳይሬክተርና ተመራማሪ አቶ ዮናስ ገብረሚካኤል ሰው ሰራሽ አስተውሎት ማሽኖችና ኮምፒተሮችን ተጠቅሞ እንደ ሰው ማሰብ፣ ማመዛዘንና መተንበይ የሚችሉ ፕሮግራሞችን የሚሰራ ስርዓት ነው ይላሉ፡፡ አሽከርካሪ አልባ መኪኖች፣ የሰብልን ጤና የሚጠቁሙ ማሽኖች የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤት መሆናቸውን ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህ ረገድ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅና ጋና ከአፍሪካ መሰረት በመጣል ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ እንደሚገኙ ይጠቅሳሉ፡፡
ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመ ሁሉት ዓመት ባይሞላውም የሰው ሀይል ቀጥሮና የአሰራር ስርዓት ዘርግቶ ስራ ጀምሯል ይላሉ፡፡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚሰጧቸውን አገልግሎቶችና ያሉበትን አድራሻ የሚጠቁም መተግበሪያ፣ የከተማ አውቶብሶች የደረሱበትን ቦታ፤ የመሳፈሪያ ጣቢያ ላይ በስንት ደቂቃ እንደሚደርሱ መረጃ የሚሰጡ ቴክኖሎጂዎችን በየአውቶብስ ማቆሚያዎች ለመስራት ፕሮጀክት ተቀርጾ ተግባራዊ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
እውነታው ይህ ቢሆንም ብዛት ያለው የሰው ሀይል ስራ አጥ በሆነባቸው ታዳጊ አገራት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ብዙም አስፈላጊ አለመሆኑን በመግለፅ ቴክኖሎጂውን የሚተቹ አካላት አሉ፡፡ ይህ ግን ውሃ የማይቋጥር እንደሆነ ነው አቶ ሳንሉካን የሚናገሩት፡፡ ‹‹ ሁል ጊዜ የቴክኖሎጂ ተከታይ መሆን አይገባም፡፡ ቴክኖሎጂዎቹ በባህርያቸው የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንቶች ናቸው፡፡ ዛሬ ውድድሩ በቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ አተኩሯል፡፡ ስለዚህ ውድድሩን ለማሸነፍ ከወዲሁ መሰረት መጣል ይገባል›› በማለት ቴክኖሎጂው በራሱ ስራ እንደሚፈጥርም አስገንዝበዋል፡፡ ቴክኖሎጂውን በመታጠቅ ለተሻለ ለውጥና ዕድገት መትጋት ይገባል፡፡

ጌትነት ምህረቴ 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።