ለቆዳ ኢንዱስትሪው ውጤታማነት ትኩረት የሚሹ ተነፃፃሪ ጉዳዮች Featured

11 Jun 2018

አገራችን በአፍሪካም ሆነ በዓለም ደረጃ ከሚነገርላት ሰፊ ሀብቷ ውስጥ የቁም እንስሳት አንዱ ነው፡፡ ከአፍሪካ በቀዳሚነት፣ ከዓለምም ከመጀመርያዎቹ አስር አገራት ተርታ ያሰለፋትን የእንስሳት ሀብቷን በአግባቡ ከተጠቀመች በኢኮኖሚ ዕድገቱ ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ይታመናል፡፡ በተለይ የእንስሳት ውጤት የሆነው የቆዳ ምርት በአግባቡ ከተሰራበት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን በማስገኘትና ሰፊ የሥራ ዕድልን በመፍጠር ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ በትኩረት ካልተሰራበትና ተገቢው እርምት ካልተደረገበት ካለው ፋይዳ አንፃርነት የሚታይ ጉልህ አከባቢያዊ ተጽዕኖ እንዳለውም እሙን ነው፡፡ በዚህ ልክ የሚገለፀው የቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በኢትዮጵያ ረዥም ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ ባለድርሻዎችም በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትና ውጤቶቻቸውን፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎቻቸውን በተመለከተ የሚናገሩት አላቸው፡፡
አቶ እንድሪስ ኢብራሂም፣ በ1918 ዓ.ም ተቋቁሞ ለረዥም ጊዜ በመንግሥት ስር ሲተዳደር የቆየውና በኋላም ወደ ግል ሲዞር በመግዛት የግላቸው ያደረጉት የአዲስ አበባ ቆዳ ፋብሪካ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ፋብሪካውን ከገዙት በኋላ ብዙ ማሻሻያዎችና ለውጦች አድርገውበታል፡፡ በበሬ ቆዳ ምርት የሚታወቀው ይህ ፋብሪካ፣ አሁን ላይ የበግና የፍየል ሌጦንም እየሰራ ሲሆን፤ ያለቀለት ቆዳን ለጫማ፣ ለጃኬት፣ ለቦርሳ፣ ለሶፋና መሰል ምርቶች ግብዓትነት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡ በቀጣይም በሰፊው ወደገበያው የመግባት ዕቅድ ይዘዋል፡፡
በዘርፉ በሚከናወኑ ተግባራት ውጤት እየታየ ቢሆንም፤ በሚፈለገው ልክ እንዳይጓዝ የሚያደርጉ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን አቶ እንድሪስ ይናገራሉ፡፡ ከእነዚህ ችግሮች መካከል አንዱ የግብዓት ችግር ሲሆን፤ ይህም ከአገር ውስጥ የሚቀርበው ጥሬ እቃን እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የኬሚካል አቅርቦትን የሚመለከት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቆዳና ሌጦ በኩል ከአቅርቦቱ ይልቅ የጥራት ችግር እጅጉን ፈታኝ መሆኑን በመጠቆምም፤ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱንና በተለይ በወጪ ንግዱ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ማሳደሩን ይገልፃሉ፡፡
የግብዓት ጥራት ችግር በምርቶች ላይ ከሚያሳድረው የዋጋ ልዩነት ባለፈ፣ ከየፋብሪካው ሳይወጡ ውድቅ የሚደረጉ ምርቶች በመኖራቸው በፋብሪካዎቹ አቅም ላይም ሆነ በአገር ገቢ ላይ ችግሩን የጎላ እንዳደረገው ያብራራሉ፡፡ ከኬሚካል አቅርቦት ጋር በተያያዘም እስከ 95 በመቶ የሚሆኑት ኬሚካሎች ከውጭ የሚገቡ እንደመሆናቸው ይሄን ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ ችግር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ይሄም በዘርፉ ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ እንድሪስ አባባል፤ የቆዳ ጥራትን ከማስጠበቅ አኳያ ሥራው ከአርብቶ አድሩና አርሶ አደሩ ቀዬ የሚጀምር እንደመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ ተቀናጅቶ ሊሰራ ይገባዋል፡፡ ጥራት ያለው ቆዳን ማግኘት የሚቻለው ከብቱ በህይወት ካለበት ጊዜ ጀምሮ በሚሰራ ሥራ እንደመሆኑም የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻዎች ከምንጩ ጀምሮ ክትትልና ድጋፍ በሚደረግበት አግባብ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ አግባብ በመሥራት ብቻ በዘርፉ የሚታየውን የውጭ ምንዛሬ ችግር ማቃለል ይቻላል፡፡ ካልሆነ ግን በትንሽ ብር በሚሰራ ሥራ የቆዳ ጥራትን ባለመጠበቅ በሚከሰት ችግር በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ በማጣት የዘርፉን የምንዛሬ ጥያቄ እንኳን መመለስ የማይቻልበት ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በመሆኑም የጥራት ችግርን በማቃለል ብቻ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን በማግኘት ዘርፉንም፣ አገርንም መደጎም ይቻላል፡፡
አቶ እንድሪስ እንደሚያብራሩት፤ የቆዳው ኢንዱስትሪ ለአገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ የጎላ ነው፡፡ በአንፃሩ የቆዳ ምርት የአካባቢ በካይነት የሚጀምረው ከእርድ ሂደቱ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው የቆዳ ሥራ ከአድካሚነቱም በላይ ለንጽህና በጣም አስቸጋሪ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም ጠቃሚነቱ ብቻ እየታሰበ አካባቢን መበከል ስለማይኖርበት ለአካባቢ ተስማሚ በሆነ መልኩ መከናወን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ አኳያ የአዲስ አበባ ቆዳ ፋብሪካ የመጀመሪያ ደረጃ ማጣሪያ አስገንብቶ ሥራ ላይ ያዋለ ሲሆን፤ 30 ሚሊዬን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ በማድረግም ሁለተኛ ደረጃ ማጣሪያ ግንባታም በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ ቢሆንም፤ ሥራው አካባቢን መሰረት ያደረገ መሆን ስላለበት አብዛናው የቆዳ ፋብሪካዎችም የመጀመሪያ ደረጃ ማጣሪያ ገንብተው ሥራ ላይ አውለዋል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ማጣሪም እየሰሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በወንዞች ላይ የሚደርስ ብክለትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የማጣሪያ ግንባታ ሥራው ዕውን መሆን የአካባቢ ጥበቃ ሥራውን የማገዝ ብቻ ሳይሆን፤ የዓለም ገበያን ሰብሮ ለመግባት እንደ ግዴታም የሚታይ ነው፡፡
አቶ እንድሪስ፣ የቆዳ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ አገራዊ ፋይዳና ሰፊ የሰው ኃይል ስለመፈለጉ፣ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያም ጉልህ ሚና ያለው ስለመሆኑ፣ አገሪቱም ከሰፊው የእንስሳት ሀብቷም ተጠቃሚ እንድትሆን እንደሚያደርጋት ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ዘርፉ ባለሀብቱን ተጠቃሚ ሳያደርግ በመቆየቱ ከፍተኛ ካፒታልና ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ይገልፃሉ፡፡ የእርሳቸው ፋብሪካ ሁለተኛ ደረጃ ማጣሪያ እየገነባ ቢሆንም፣ ከመሬት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግር እያጋጠመው መሆኑን በማሳያነት በማንሳትም፤ ባለሀብቱ አገራዊ ግዴታውን ለመወጣት በዘርፉ ሲሰማራ ከመንግሥት ሰፊ ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡ በመሆኑም በዚህና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ የዘርፉ ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ተናጥላዊም ሆነ የጋራ ችግሮች ለይቶ በጋራ መሥራትና ለችግሮቻቸው መፍትሄ ማበጀት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ፡፡
የኢትዮጵያ ቆዳ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ታጠቅ ይርጋ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የቆዳ ሥራ ዘርፉ በኢትዮጵያ ከመቶ ዓመት የዘለለ ታሪክ ያለው ቢሆንም ዛሬም ድረስ በሚፈለገው ልክ ውጤት እየታየበት አይደለም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዘርፉ ከፍተኛ ችግር ያለበትና የወጪ ንግዱም ከዓመት ዓመት እየቀነሰ የመጣ ነው፡፡ ከእነዚህ ችግሮች መካከል አንዱና ትልቁ ችግር የቆዳ ፍሳሽ ማጣሪያ ሲሆን፤ ፋክሪካዎች አካባቢን እየበከሉ መቀጠል እንደሌለባቸው በማመን ችግሩን ለማቃለል ሀብታቸውን አፍስሰው የማጣሪያ ግንባታ እያከናወኑ ናቸው፡፡ ሁለተኛው ችግር የቆዳ ግብዓት ጥራት ሲሆን፤ ለዚህ ችግር መቃለልም ከግብርናው ዘርፍ ተቋማት ጋር በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
አቶ ታጠቅ እንደሚናገሩት፤ ከውጭ ማሽነሪዎች በማስገባት ጭምር የፍሳሽ ማጣራት ሥራው በሰፊው እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ከጥሬ ቆዳ ጥራት ጋር በተያያዘም ያለው ችግር ዘርፉ የሚፈለገውን ያክል እንዳይጓዝና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆን እያደረጋት በመሆኑ ችግሩን ለማቃለል ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በዚህም የቆዳን ጥራት ለማምጣት እንስሳቱ ከመጀመሪያው አንስቶ ተገቢው እንክብካቤ እንዲደረግላቸው የሚያስችሉ አሰራሮች ዙሪያ ከመንግሥት ጋር ይሰራል፡፡ ለውጤታማነቱም ባለሀብቱ ከሚያደርገው ጥረት በተጓዳኝ መንግሥት በሚገባ መደገፍና ቀጣይነት ባለው መልኩ መሥራት ይኖርበታል፡፡
የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዱ ለገሰ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ በቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰራው ሥራ ውጤት እያሳየ ነው፡፡ በዚህም ቆዳን በጥሬው ለገበያ ከማቅረብ ይልቅ እሴት ጨምሮ የተሻለ ዋጋ የሚገኝበትን ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡ በአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ሳይቀር የሚመረቱ የተለያዩ የቆዳ ውጤቶች ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እየቀረቡ፤ ውጤቱም ከዓመት ዓመት እየጨመረ ይገኛል፡፡ ለውጡም በፖሊሲዎችና በቴክኖሎጂ ድጋፎች ታግዞ ለረዥም ጊዜ በተሰራ ሥራ ውጤት ነው፡፡
በዚህ መልኩ የሚታይ ውጤት ቢኖርም ዘርፉ አሁንም ሰፊ ችግር ያለበት መሆኑን ያልሸሸጉት አቶ ወንዱ፤ ከግብዓት፣ ከውጭ ምንዛሬና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ያሉ ችግሮች ተለይተው እየተሰራባቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ እንደ እንደሳቸው ገለፃ፤ ከጥሬ ዕቃ ግብዓት ጋር የሚያያዘው አንድ የግብዓት ችግር ሲሆን፤ በዚህ ረገድ የሚስተዋለው የቆዳ ጥራት ችግር ከእንስሳቱ የአረባብና እንክብካቤ ባህል ጋር የሚከሰት እንደመሆኑ ለችግሩ መቃለል የግብርናው መስሪያ ቤት እየሰራበት ነው፡፡ የሚመጡ ቆዳዎችንም አሻሽሎ ጥራታቸውን ማሳደግ በሚቻልበት ዙሪያ ከኢንዱስትሪዎች ጋር እየተሰራ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ መሥራትን ይጠይቃል፡፡
ከኬሚካል አቅርቦት ጋር በተያያዘም የቆዳ ፍብሪካዎች ችግር ማለት የአገር ችግር ማለት እንደመሆኑ፤ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ኬሚካል አስገብተው ካልሰሩ በስተቀር ቆዳን ማልፋት አይችሉም፤ በተመሳሳይ የጫማና ሌላም ምርት ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን በሚፈለገው መልኩ ለማውጣት የተለያዩ ግብዓቶችን ይፈልጋሉ፤ ለዚህ ደግሞ የውጭ ምንዛሬ የግድ ይላል፡፡ ሆኖም ኢንዱስትሪዎቹ የውጭ ምንዛሬ ችግር ስላለባቸው ቶሎ ማግኘት አይችሉም፡፡ ይሄን ምንዛሬ ቆይቶ ማግኘትና ቶሎ ማግኘት በራሱ በወጪ ገበያው ላይ የሚያሳድርባቸው ተጽዕኖ አለ፡፡ ይሄን ችግር በመገንዘብም መፍትሄ ለማምጣት በመንግሥት በኩል በርካታ እርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው፡፡
የኢንዱስትሪዎቹን የውጭ ምንዛሬ ችግር ለመፍታት የውጭ ምንዛሬ እንዲጨምር ከሚሰራው ሥራ በተጓዳኝ፤ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ዙሪያ ያለውን ችግር ለማቃለልም ሰብ ስቴሽኖች እንዲገነቡ በማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ ከቴክኖሎጂ አቅም ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ለማቃለልም ከሌሎች በማስገባት ለቆዳ ፋብሪካዎች የማስተላለፍና የማላመድ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡
እንደ አቶ ወንዱ ማብራሪያ፤ የአካባቢ ብክለት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ያለ ሳይሆን፤ በሁሉም ዓለም ላይ እስካሁንም ድረስ ያለ ችግር ነው፡፡ ችግሩም በአንድ ጊዜ መፍትሔ የሚገኝለት ባይሆንም፤ ለችግሩ መፍትሄ የሚሆን ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ የሚያስችሉ የበካይ ኬሚካሎችና ቆሻሻዎችን ማጣሪያ ግንባታ አንዱ ሲሆን፤ የቆዳ ፋብሪካዎቹ የአንደኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ የማጣሪያ ግንባታ ሥራ እያከናወኑ ናቸው፡፡ መንግሥትም እየደገፈ ሲሆን፤ ኬሚካሎች ቆዳው ውስጥ እንዲቀሩ የሚያደርጉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ጭምር በመተግበር ቆሻሻን ከምንጩ የመቀነስ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ በመሆኑም በባለሀብቱ በኩል ለዚህ ተግባር ውጤታማነት በቁርጠኝነት መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥትም በፖሊሲም ሆነ በፋይናንስ የመደገፍ አሰራሮችን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡  

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።