በፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደረው የአመራርና የባለሙያ ቁርጠኝነት ማነስ Featured

12 Jun 2018

በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች የከተሞች የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት እየተካሄደ ይገኛል፡፡በፕሮጀክቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የድንጋይ ንጣፍ (cobblestone) መንገድ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች ፣ የፍሳሻና ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ፣የገበያ ቦታ ማሻሻል ፣የፓርክ ልማት ፣ የድልድይና የውሃ መውረጃ ቦይ፣ የውስጥ ለውስጥ የጠጠር መንገዶች፣ የመንገድ መብራት ፣የወንዝ ገመገም መከላከያ ፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የእግረኛ መንገድ እና የአውቶብስ መናኸሪያ ሥራዎች ናቸው፡፡በዚህም በአንደኛው የከተሞች የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት በርካታ ተግባሮች ተከናውነዋል፡፡
ሁለተኛው የከተሞች መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይህ ፕሮግራም ከአዲስ አበባ በስተቀር 26 አዳዲስ ከተሞችን በመጨመር በአጠቃላይ በ44 ከተሞች በ556 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ነው የሚተገበረው ፡፡
የኢፌዴሪ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ዓመታዊ የከተሞች መገምገሚያ መስፈርቶችን በማዘጋጀት የ2009 እና 2010 ዓ.ም የከተሞች የፕሮጀክት አፈፃጸም ሰሞኑን ገምግሟል፡፡ የግምገማውን አንኳር ነጥቦችና ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስመልክቶ በኢፌዴሪ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የከተሞች ገቢ ማሻሻያ ፈንድ ሞቢላይዜሽንና ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ አምላኩ አዳሙ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
የሁለተኛው የከተሞች መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም አጠቃላይ የፕሮጀክት አፈፃፀም
በ2007 ዓ.ም ከተያዙት ፕሮጀክቶች ውስጥ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ በጥሩ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ከተሞች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥም ከክልሎች የትግራይ ክልልን እንዲሁም በከተማ ደረጃ ጅግጅጋ ይጠቀሳል፡፡ ደካማ የፕሮጀክት አፈፃፀም ከታየባቸው ደግሞ ጋምቤላና የሀረሪ ክልል ይገኙበታል፡፡
በ2008 ዓ.ም በክልል ደረጃ አማራ ከ2007 ዓ.ም በተሻለ መልኩ ፕሮጀክቶችን በመፈፀም ትልቅ ለውጥ እምጥቷል፡፡ የኦሮሚያ ክልል በአንፃሩ በ2007 ዓ.ም ከነበረው አፈፃፀም ዝቅ ብሎ ተገኝቷል፡፡ ይህ የሆነበትም ዋነኛ ምክንያት በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ሰላምና መረጋጋት ባለመኖሩ ነው፡፡ የአመራር ቁርጠኝነት መሳሳትም በፕሮጀክት አፈፃፀሙ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በ2007 ዓ.ም የነበረውን ዝቅተኛ አፈፃፀም አሻሽሏል፡፡ትግራይ እንደ ክልልና ጅግጅጋ እንደ ከተማ በፊት ከነበራቸው የፕሮጀክት አፈፃፀም በመጠኑ ቀንሰዋል፡፡
በ2009 ዓ.ም የከተሞች የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ሲታይ አንዳንድ ልምድ ያላቸው ከተሞች ጥሩ አፈፃፀም አሳይተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የአማራ ክልል ከተሞች ይገኙበታል፡፡ከክልሉ 11 ከተሞች ውስጥ 91 በመቶው ፕሮጀክታቸውን አጠናቀዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ካላቸው ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ሌሎችንም በማካተት ከእቅድ በላይ ፈፅመዋል፡፡ ይሁን እንጂ የአሶሳና የጋምቤላ ከተሞች የፕሮጀክት አፈፃፀም ዝቅተኛ እና አሳሳቢ ሆኗል፡፡ በ44 ከተሞች ከተያዙ ፕሮጀክቶች ውስጥ 2ሺ679 ፕሮጀክቶች ለማከናወን ታቅዶ 2ሺ368 ወይም 88 በመቶውን መፈፀም ተችሏል፡፡
የ2010 ዓ.ም የአስር ወር የፕሮጀክት አፈፃፀም ሲገመገም በሁሉም ከተሞች ላይ ቁልፍ ችግሮች ታይተዋል፡፡ ለዚህም ተጠቃሹ ምክንያት በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ሰላምና መረጋጋት ባለመኖሩና ፕሮጀክቶቹን ለማከናወን የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ ባለመፈጠሩ ነው፡፡ በአመራሩ በኩል ፕሮጀክቶችን ለመፈፀም ቁርጠኝነት ማነስም ለፕጀክቶቹ በጊዜ አለመጠናቀቅ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል፡፡
የሠራተኛ በተደጋጋሚ መልቀቅ ፣ በአንዳንድ ክልሎች የከተማ አመራሩም ሆነ ሙያተኛው በየጊዜው መቀያየር፣ ፕሮግራሙን መፈፀም የሚችል ጠንካራ አደረጃጀት በከተሞች አለመኖር፣ የማስፈፀም አቅምና የአመራር ብቃት ማነስም በፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም ላይ ተፅዕኖ አሳድረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከጅግጅጋ ከተማ በስተቀር ሌሎቹ ፕሮጀክታቸውን ከሃምሳ በመቶ በታች ነው ፈጽመው የተገኙት፡፡
ክልሎቹና ከተሞቹ የተለያየ አፈፃፀም ሊኖራቸው የቻለበት ምክንያት
የፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም ክልሎች እንዳላቸው የከተማ ብዛትና የፕሮጀክት ብዛት ይወሰናል፡፡ የየከተሞቹ ፕሮግራሙን የማስፈፀም አቅምና የአመራር ቁርጠኝነትም በፕሮጀክት አፈፃፀሙ ላይ ልዩነት እንዲኖር አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
ፕሮጀክቶችን በመፈፀም ረገድ በክልልም ሆነ በከተማ ደረጃ በርካታ አመርቂ ሥራዎች የተሰሩ ቢሆንም ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብና እቅድ መሰረት ሙሉ በሙሉ ከመፈፀም አንፃር ግን የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት አልተቻለም፡፡ በየደረጃው ያለው አመራርና ባለሙያ ቁርጠኛ ሆኖ ቢሰራ ኖሮ ፕሮጀክቶቹን ሙሉ በሙሉ መፈፀም የሚቻልበት ዕድል ሰፊ ነበር ፡፡
በተደጋጋሚ ዝቅተኛ የሆነው የጋምቤላ ከተማ የፕሮጀክት አፈፃፀም
የጋምቤላ ክልል በተደጋጋሚ ፕሮጀክቶችን በመፈፀም ረገድ አፈፃፀሙ ዝቅተኛ ሊሆን የቻለው የአመራር ቁርጠኝነት ችግሮች በመኖራቸው ነው፡፡ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል የሚደረጉ ድጋፎችን ተጠቅሞ አደረጃጀትን በማስተካከልና ህብረተሰቡን በማሳተፍ ፕሮግራሙን ውጤታማ ለማድረግ ያለውን አቅም አሟጠው ሊጠቀሙ አልቻሉም፡፡ በዚህም ምክንያት ክልሉ በ2008 ዓ.ም ከፕሮግራሙ እስከ መውጣትም ደርሶ ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅትም ክልሉን በተለየ መልኩ መደገፍ እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ሃዋሳ በዚህ ፕሮግራም ላይ ለውጥ እያመጣች ያለች ከተማና የጋምቤላ እህት ከተማ በመሆኗ እንድትደግፍ ኃላፊነት ተሰጥቷታል፡፡
ፕሮግራሙ ውጤታማ እንዳይሆን
ያደረጉ ክፍተቶች
ከክልል እስከ ከተማ የሚገኘው አመራር በቁርጠኝነት ፕሮግራሙን መያዝና ማስፈፀም አልቻልም፡፡ የክልል የሚመለከታቸው ቢሮዎች በቅንጅት የተሟላ ድጋፍና ክትትል አላደረጉም፡፡ ፕሮግራሙን መፈፀም የሚችል ጠንካራ አደረጃጀት በከተሞች አልተፈጠረም፡፡
የአካባቢና ማህበራዊ ደህንነት ጉዳዮች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የጎላ ስለመሆኑ በየደረጃው ያለው አመራር የተሟላ ግንዛቤ ሊኖረው አልቻለም፡፡ አመራሩ አፈፃፀማቸው ዝቅተኛ ለሆኑና መዘግየት ለታየባቸው ፕሮጀክቶች የተለየ ትኩረት በመስጠት ድጋፍና ክትትል አላደረገም፡፡ በዚህም ፕሮጀክቶች ወደቀጣይ በጀት ዓመት ተሸጋግረዋል፡፡ የፕሮጀክት አፈፃፀም አዝጋሚ እና የበጀት አጠቃቀምም አነስተኛ ሆኗል፡፡ የከተሞች የገቢ አሰባሰባቸው ከእቅድ አንፃር አነስተኛ ሆኖ በመገኘቱም በእቅዱ መሰረት ጠንክሮ ገቢን መሰብሰብ አልተቻለም፡፡ የዕቅድና የሪፖርት አቀራረብ የተቀናጀ ያለመሆን ፣ በክልልና በከተሞቹ ወቅታዊና የተደራጀ መረጃ አያያዝ ሥርዓት በተገቢው ሁኔታ ያለመኖርና ሌሎችም ፕሮጀክቶቹ በአግባቡ እንዳይፈፀሙ ተፅዕኖ ያሳደሩ ችግሮች ናቸው፡፡
የፕሮጀክት አፈፃፀሙን ለማሻሻል
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያለው የክትትል ቡድን በዘንድሮው በጀት አራት ጊዜ መስክ በመውጣት ለከተሞች ልዩ ድጋፍ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ ፕሮግራሙ በቀጣይ ዓመት የሚጠናቀቅ በመሆኑም ከተሞች የተመደበላቸውን በጀት በአግባቡ መጠቀም ካልቻሉ ያልተጠቀሙበት ገንዘብ ተመላሽ ስለሚሆን እንዲጠቀሙበት ግፊት ተደርጓል፡፡እቅድ አዘገጃጀት ላይ የጥራት ጉድለት በመኖሩ ከተሞች ብቃትና ክህሎት ያለው እቅድ በስታንዳርዱ መሰረት ማዘጋጀት እንዲችሉ በተደጋጋሚ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ለአመራሮችና ለባለሙያዎች ተሰጥቷል፡፡
ለፕሮጀክት ማከናወኛ የሚሆን በጀት ለከተሞች በቶሎ እንዲለቀቅ የራሳቸውን በጀት ያፀደቁ ክልሎች ሌሎች ክልሎችን መጠበቅ ስለማይኖርባቸው በጀቱ ለከተሞቹ በቶሎ የሚደርስበት ሁኔታ እንዲመቻች ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጋር መግባባት ያስፈልጋል፡፡ ካለው የኑሮ ውድነትና ከፕሮጀክቱ አድካሚነት አንፃር የክልል የአማካሪ ቡድን ደመወዝ ማስተካከያ ለማድረግ ተሞክሮ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ወደፊት ግን ይህ የሚስተካከልበት ሁኔታ ይመቻቻል፡፡
ከፕሮጀክቶች ጥራት ጉድለት ጋር በተያያዘ የሚገነቡ መሰረተ ልማቶች ምን ያህል ጥራት እንዳላቸው በፌዴራል የክትትል ቡድኑ አማካኝነት በየከተሞቹ በመዘዋወር እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶች በተጨባጭ በስታንዳርዱ መሰረት እየተከናወኑ ስለመሆኑም ክትትል ተደርጓል፡፡ እነዚህንም ጉዳዮች ከተሞቹ በባለቤት በመወሰድ ሊሰሩ ይገባል፡፡ የግንባታ ሥራዎች ላይ የጥራት መጓደል ሲኖር ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች በውላቸው አካታው መሄድ ይኖርባቸዋል፡፡ ለአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የሚሰጡ ሥራዎች ጥራትን አስጠብቀው እንዲሰሩ ማድረግ እንዲሁም የአነስተኛና ጥቃቅን ማህበራት አባላትን ክህሎት መገንባት ያስፈልጋል፡፡በዚህ ረገድ ከተሞች የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ ከማስገባታቸው በፊት አቅማቸውን መገንባት ይኖርባቸዋል፡፡
ፕሮግራሙን በተሻለ መልኩ ለመፈፀም
የተቀመጡ አቅጣጫዎች
ፕሮጀክቶቹ በወቅቱ መጠናቀቅ ሲገባቸው ባለመጠናቀቃቸው የመልካም አስተዳደር ችግር መሆናቸው የማይቀር ነው፡፡ ህብረተሰቡ ሊጠቀምበት የሚችለውን ዕድል የበለጠ የሚያሳጣ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ክፍተት እንዳለ ተገምግሟል፡፡ በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት የከተሞች የፕሮጀክት አፈፃፀም በጥንካሬና በድክመት ተለይቷል፡፡ በዚህ ዓመት መጠናቀቅ ያለባቸው ፕሮጀክቶች ወደ ቀጣዩ ዓመት እንዳይሸጋገሩም ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ለዚህም የ44ቱ ከተማዎች ከንቲባዎችና የየክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ኃላፊዎች ፕሮግራሙ ሊጠናቀቅ መሆኑን በመረዳት ፕሮጀክቶቻቸውን በታሰበው ጊዜ ለማጠናቀቅ ቁርጠኝነታቸውን ገልፀዋል፡፡
ከተሞች በቀጣይ ፕሮጀክቶቻቸውን መፈፀም የሚያስችላቸውን እቅድ እንዴት ማዘጋጀት እንዳለባቸው መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ በዚህም መሰረት ከተሞቹ የሦስት ዓመት እቅድ እንዲያዘጋጁ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡ ፕሮግራሙን ለመምራት የፌዴራል ስትሪንግ ኮሚቴና የየክልሉ የስትሪንግ ኮሚቴ ጠንካራ የጋራ ፎረም ለመመስረት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ በየከተሞቹ ያሉትን አፈፃፀሞች እያንዳንዱ የክልል ስትሪንግ ኮሚቴ መቆጣጠርና መምራት እንዳለበትም መግባባት ተችሏል፡፡
ከተሞች ፕሮጀክቶቻቸውን ለማስኬድ የሚያስችላቸውን ገቢ በአግባቡ እየሰበሰቡ አይደለም፡፡ በመሆኑም በየክልሉ የሚገኙ የገቢ ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች ከተሞች ገቢያቸውን እንዳይሰበስቡ ያላስቻላቸውን የክህሎትና የአቅም ክፍተት በመለየት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡ በፕሮጀክቶች ክንውን ሂደት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ አካባቢያዊና ማህበራዊ ደህንነት ጥበቃ ጋር በተያያዘ ደግሞ የየክልሉ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አፅንኦት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡ በአጠቃላይ የስትሪንግ ኮሚቴ አባላት ለፕሮግራሙ ስኬት ጠንካራ ሆነው በጋራ መስራት እንዳለባቸው አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።