‹‹በ21ኛው ክፍለ ዘመን መንግሥት መሬትን ለብቻው ይዞ ፊውዳል መሆን የለበትም›› - ዶክተር ጌታቸው ድሪባ የግብርና ኢኮኖሚ ተመራማሪና ምሁር Featured

13 Jun 2018

ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪ፣ ከጀርመን ዶርቱሙንድ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪ፤ እንዲሁም ከእንግሊዙ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኢስት አንግሊያ ሦስተኛ ዲግራቸውን በግብርና ኢኮኖሚክስ ይዘዋል፡፡ በአገር ውስጥ በፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅነት የጀመረው የሥራ አገልግሎት እስከ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድረስ ዘልቋል-ዶክተር ጌታቸው ድሪባ፡፡
ዶክተር ጌታቸው በኬር ኢትዮጵያና ኬር ኢንተርናሽናል ዓለም አቀፍ የተራድዖ ድርጅት፤ በላይቤሪያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተርና ተወካይ፤ በደቡባዊ አፍሪካ፣ በመካከለኛውና በታላላቅ ሃይቆች/ግሬት ሌክስ/ አገራት በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በመካከኛው አውሮፓና በዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና መሥሪያ ቤት የአጋርነትና አቅም ግንባታ ልማት አገልግሎት ኃላፊ፣ በሱዳን የፕሮግራም አማካሪ በመሆን ሠርተዋል፡፡ በቻይና የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተርና የፕሮግራሙ ተወካይ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ በቤጂንግ የተቋሙ የልህቀት ማዕከል እንዲከፈትም አድርገዋል፡፡
በግብርና ዙርያ ያተኮሩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የምርምር ውጤቶችና ጥናቶችን በማካሄድ ለህትመት አብቅተዋል፡፡ በቅርቡም የኢትዮጵያን የግብርና ጅማሮ፤ ተግዳሮትና የመፍትሔ ምክረ ሃሳቦችን የያዘ ‹‹Overcoming Agricultural and Food Crises in Ethiopia›› የሚል መፅሐፍ በማዘጋጀት ለንባብ አብቅተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ግብርና ዙርያ ከዶክተር ጌታቸው ሠፋ ያለ ቆይታ አድርገናል፤ እነሆ፡-

አዲስ ዘመን፤ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያለችበትን ደረጃ እንዴት ይገልፁታል?
ዶክተር ጌታቸው፤ ኢትዮጵያ ያለችበት የግብርና ደረጃ እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ ዓለም ትልቅ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት ኢትዮጵያ ከ10 ሺ ዓመት በፊት ከነበረው አሠራር አልተላቀቀችም፡፡ ማረሻ፣ ዶማ፣ አካፋና በሬ በመጠቀም ነው እየተመረተ ያለው፡፡ ምርቱ በአህያ እየተጓጓዘ፣ በባህላዊ ጎተራ ከመጠራቀም አሰራር አልዘለለም፡፡
መንግሥትም ምርትን ለማሳደግ የሚሰራው መሬትን በማስፋት ነው፡፡ ጫካው እየተመነጠረ መሬቱ እየሰፋ መሆኑም ግልፅ ነው፡፡ ምርቱም ማደጉ አይካድም፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ 100 ሚሊዮን ህዝብ መመገብ አይቻልም ነበር፡፡ አሰራሩ ግን የቀድሞውን ይዞ የሚሄድ በመሆኑ መዋቅራዊ ለውጥ የሚያመጣ አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ ራሷን ከቀበረችበት ቀና አድርጋ ብታይ ዓለም ብዙ ርቋት ሂዷል፡፡ ኢትዮጵያ ከ10ሺ ዓመት በፊት የነበረውን ቴክኖሎጂ ይዛ ነው ያለችው፡፡ በጥገና የእርሻ ሥርዓት 100 ሚሊዮን ህዝብ መመገብ ከባድ ነው፤ አይቻልም፡፡
በአሁኑ ወቅት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የአንድ ሰው ምርታማነት በሚደንቅ ደረጃ አድጓል፡፡ በኢትዮጵያ አንድ አርሶ አደር ወቅትና ሁኔታዎች ተመቻችተውለት አንድ ሄክታር ቢያርስ ከፍተኛው 25 ኩንታል ነው፡፡ የአብዛኛው አርሶ አደር መሬት ግን ከግማሽ ሄክታር አይበልጥም፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እዚህ ደረጃ ላይ መሆኑ አሳዛኝም፤ አሳፋሪም ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ኢንዱስትሪው ስላዞረች ይሆን እርሻው ደካማ ሆኖ የቀጠለው?
ዶክተር ጌታቸው፡- ዓለም የኢንዱስትሪ አብዮት ውስጥ ከገባ ከ200 ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዕድገት እጅግ ኋላ ቀር ነው፡፡ አሁን እንዲያውም የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመገንባታቸው ነው ስለ ኢንዱስትሪ የሚወራው፡፡ ይህም ቢሆን የእርሻ ውጤቶችን በግብዓትነት ይዞ የሚሄድ አይደለም፡፡ እርሻውን የሚያዘምን የኢንዱስትሪ ዕድገት ባለመሆኑ ኢንዱስትሪና እርሻው አልተጣጣሙም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግብርናው ለመዳከሙ በእርስዎ ጥናት ምክንያቱ ምንድን ነው?
ዶክተር ጌታቸው፡- ለግብርናው ተገቢ ትኩረት አልተሰጠም፡፡ የገጠሩ ወጣት መሬቱ እየተበጣጠሰ ወደ ከተማ እየፈለሰ ነው፡፡ ይሄ ፍልሰት የፖለቲካ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የትምህርት ተቋማት፣ የቴክኖሎጂ አንቀሳቃሾችን እንዴት እንቅልፍ ይወስዳቸዋል የሚያስብል ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከባለፉት ሠላሳ ዓመታት ጀምሮ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ስንዴ ከውጭ እያስገባች ነው፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ባለው መረጃ መሰረት በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር በሚጠጋ ወጪ ስንዴ ይገዛል፡፡ እነ ዘይትና ስኳር ቢጨመሩ ወጪው ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡
በአንድ በኩል ፈጣሪ የለገሰንን ቡና ሸምጥጠን ለውጭ ገበያ አቅርበን የውጭ ምንዛሪ ስናገኝ፤ በአገራችን ማምረት ያቃተንን ስንዴ ለመግዛት ደግሞ የውጭ ምንዛሬ እናወጣለን፡፡ ይሄ ብቻውን ግብርናው ላይ ብዙ እንዳልተሰራ በግልፅ ያሳያል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወጣቱ በገጠር ካለው አድካሚ የእርሻ ሥራ ይልቅ በከተማ የራሱን ሥራ ለማንቀሳቀስ ፈልጎ መምጣቱ ለፍልሰቱ ምክንያት አይሆንም?
ዶክተር ጌታቸው፡- የእርሻ ሥራ አድካሚ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ወጣት ለብዙ ጊዜ አባቱን በመተካት በእርሻ ላይ ተሰማርቶ አሳልፏል፡፡ አሁን ግን ነገሩ ተቀይሯል፡፡ ለዚህም ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ አንዱ መሬቱ ተበጣጥሶ በማለቁ፤ እርሻውን ለመሥራት አለመቻሉ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ እርሻ የድህነት ምንጭ ሆኗል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት የትምህርት መስፋፋት ነው፡፡ ትምህርት ሲስፋፋ የአስተሳሰብና የልህቀት ዕድገት ይመጣል፡፡ ይህን ተከትሎ ወጣቱ ከእርሻ ይልቅ በሌላ ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት ያድርበታል፡፡ ስለሆነም ወጣቱ በዚህ ዕድሜውና ጉልበቱ ደሃ መሆን ስለማይፈልግ ፊቱን ወደ ከተማ ያዞራል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የወጣቱ ፍላጎት ከእርሻ ይልቅ የከተማ ሥራን መርጧል እያሉ ነው?
ዶክተር ጌታቸው፡- እንደነገርኩህ ግብርናው ትኩረት ስለተነፈገው ሥራ ፈጣሪ ሳይሆን የድህነት ምንጭ በመሆኑ ነው ወጣቱ ፊቱን ወደ ከተማ የሚያዞረው፡፡ በፊት እርሻ እንደ ስፖንጅ እየመጠጠ ለብዙዎች የሥራ ዕድል ፈጥሮ ነበር፡፡ አሁን ስፖንጁ ሞልቶ እየፈሰሰ ነው፡፡ ይህ ሞልቶ የፈሰሰው ኃይል ወደ ከተማ እየፈለሰ ለመንግሥት ችግር እየፈጠረበት ነው፡፡ ይህ ደግሞ አፋጣኝና ዘላቂ መፍትሔ ካልተሰጠው መጭው ጊዜ በጣም አስቸጋሪ፣ የተወሳሰበ፣ የኢትዮጵያን ህልውናን የሚፈታተን ችግር መሆኑን በቅንጭቡ የሚያሳይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የግብርናው መዳከም ባለፈው በአገሪቱ ተከስቶ ለነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ይሆናል ማለት ነው?
ዶክተር ጌታቸው፡- ንጉሡን የጣለው የአርሶ አደር አብዮት ነው፡፡ አርሶ አደሩ ኃይልና ሥልጣን ባይኖረውም ልጆቹ ከወታደር ጋር ተጋግዘው ሥርዓቱን ጥለዋል፡፡ ደርግንም አርሶ አደሩ በቃኝ በማለቱ ነው ኢህአዴግ ያሸነፈው፡፡ ኢህዴግን ወደ ሥልጣን ያመጣው እስከ አሁንም ሥልጣን ላይ ያቆየው አርሶ አደሩ ነው፡፡ አሁን ያለው እንቅስቃሴም የአርሶ አደሩ ልጅ ግፊት ነው፡፡ ይህን በጥሞና ማየት ይገባል፡፡ የፖለቲካል ኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ መሥራት ይገባል፡፡
ከተመሳሳይ ማህበረሰብና አስተሳሰብ የወጡትና በተለያየ ዕድሜ ላይ የሚገኙት የኢትዮ -ጅቡቲ ባቡርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዕድገት ለምን እንደተለያየ በደንብ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ አየር መንገድ ውጤታማ የሆነበትን ሥርዓት በሌሎቹ ለመተግበር መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በግብርናውም የዚህ ዓይነት ውጤታማ ባህል ማዳበር ያስፈልጋል፡፡
ያለፈ ታሪክን መመልከት ያስፈልጋል፡፡ የግብርናው መዳከም የአክሱም መንግሥት እንዲወድቅ አድርጓል፡፡ ከዛሬ 60ና 70 ዓመት በፊት የነበረው ችግርና ረሃብ የሰሜኖቹ እየተባለ እንደ አገር አለመታየቱ ከዛ በኋላ ሁለት ትላልቅ የረሀብ ገጠመኞችን ለማስተናገድ አስገድዷል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብን ለምግብ ድቀት ዳርጓል፡፡
ሥልጣን ላይ ያሉት የኢትዮጵያ መሪዎች ቆም ብለው ሊያስቡና ትልቅ ራዕይ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ እስከ 100 ዓመት የሚጠቅም ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ የመሬት ሥርዓቱ እንደ ህብረተሰቡ ፍላጎትና ሥርዓት እየተለወጠ መሄድ አለበት፡፡ በንጉሡ ዘመን የመሬት ሥርዓት አመቺ አለመሆኑ ‹‹መሬት ላራሹ›› የሚል አብዮት አስነስቷል፡፡ የአሁኑን የመሬት ሥርዓትም መፈተሽ ይገባል፡፡ መሬት የሀብት ማፍርያ መሆን አለበት፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን መንግሥት መሬትን ለብቻው ይዞ ፊውዳል መሆን የለበትም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግብርናውን የሚፈለገው ደረጃ ላይ በማድረስ ተጠቃሚ ለመሆንና ወደ ከተማ የሚደረገውን የወጣቱን ፍልሰት ለማስቀረት ምን መሰራት አለበት?
ዶክተር ጌታቸው፡- እርሻውን ትራንስፎርም ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ፣ ትራንስፖርትና የማከማቻ ሥርዓትን መዘርጋት ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ብዙ ምርት ይገኛል፤ ወጣቱ በስፋት ይሳተፋል፡፡ ለምሳሌ የዶሮና የወተት ላሞች እርባታ፣ የወተት ተዋፅዖ፣ የዘይት ምርት፣ የሥጋ ከብቶችን ማድለብን የመሳሰሉ ግብርናዎችን መተግበር የወጣቱን የግብርና ተሳትፎ ያሳድገዋል፡፡
በአውሮፓ፣ ቻይናና ብራዚል ግብርናው ስለዘመነ ወጣቱ በዘመናዊ ግብርና በስፋት ይሰማራል፡፡ በእነዚህ አገራት ግብርና ከሌላው ኢንዱስትሪ እኩል ነው የሚታየው፡፡ እናም ግብርና ተፈልጎ የሚገባበት ዘርፍ ነው፡፡ ዘመናዊ የእርሻ ሥርዓትን በመዘርጋት ወጣቱ በስፋት እንዲሳተፍ መሥራት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ እርሻውን ሜካናይዝ ማድረግ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው፡፡
እርሻ የጨለማ ኑሮ አለመሆኑን ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ከተማ ውስጥ ያለው ነዋሪ ውሃና የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያገኝ ሁሉ ገጠር ያለውም ይህን መሰረተ ልማት ማግኘት አለበት፡፡ በገጠሩ አካባቢ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያና መንገድን ማስፋፋት ይገባል፡፡ ዋና ከተሞች ላይ የሚሰጠው ትኩረት ለታችኞቹ ከተሰጠና የሚያስፈልገው ከተሟላ ወጣቱ መሃል ከተማን አይናፍቅም፡፡ አርሲ አካባቢ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ጨርሶ ወደ ዘመናዊ እርሻ በመግባት 15 ሄክታር መሬት የሚያርስ ወጣት አግኝቻለሁ፡፡ ይሄ ቴክኖሎጂው ወጣቱን መያዝ እንደሚችል ያሳያል፡፡
ከኢንዱስትሪው ጋር ተጣጥሞ የሚሄድ የገጠር ኢንዱስትሪ ሥርዓት በጣም አስፈላጊና ወሳኝ ነው፡፡ የገጠር ኢንዱስትሪ (አግሮ ፕሮሰሲንግ) ሲስፋፋ ግብርናውና ኢንዱስትሪው ይመጋገባሉ፡፡ ለምሳሌ ዘይት ለማምረት የቅባት እህል ያስፈልጋል፡፡ እህሉን የሚያመርቱ ብቻ ሳይሆን እህሉን በግብዓትነት ተጠቅመው ዘይት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች እንዲስፋፉ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በወተት፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍም እንዲሁ ከተሰራ ከውጭ የሚገባውን ምርት በአገር ውስጥ መተካት ይቻላል፡፡ ኢንዱስትሪው ይለማል፣ እርሻ ይስፋፋል፤ ከተሞች ያድጋሉ፤ የከተማውን ገበያ ያረጋጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አብዛኛው አርሶ አደር አነስተኛ መሬት እንዳለው በጥናት ማረጋገጥዎን ፅፈዋል፡፡ በእነዚህ በተበጣጠሱ ማሳዎች ላይ የግብርና ሜካናይዜሽንን ማካሄድ አስቸጋሪ አይሆንም?
ዶክተር ጌታቸው፡- ሜካናይዜሽንን በተበጣጠሰ መሬት ላይ ማካሄድ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለሆነም መሬቱን በማጣመርና በማዋሀድ ሰፊ የእርሻ መሬት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን ታዲያ የመሬትና የንብረት ባለቤትነትን ጨምሮ ሌሎችም መብቶች በዚህ ሂደት ውስጥ መካተትና መከበር ይኖርባቸዋል፡፡
መንግሥት የተወሰኑ አርሶ አደሮችን በማደራጀት መሬቱን በማስፋት ለማሰራት ሞክሯል፡፡ ውጤቱ በጣም ጥሩ ቢሆንም ዘለቄታዊ ለውጥ አያመጣም፡፡ ይህ ሥራ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር እንጂ፤ የአንድ ወቅት ጥገናዊ ለውጥ መሆን የለበትም፡፡ አርሲና ባሌ አካባቢ ከ200 ሺ የማይበልጡ አርሶ አደሮች ትራክተር እየተጠቀሙ ነው፡፡ እነዚህ ከአምስት እስከ 10 ሄክታር መሬት ይዘው የሚያርሱ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ሽግግርን የምታየው ኮሜርሻላይዜሽን በሚል ነው፡፡ የውጭ አገር ባለሀብቶችን በሰፋፊ እርሻው የማሰማራት ሥራ ነው ያለው፡፡ ይህ ያረጀ አስተሳሰብ ኢትዮጵያውያን እጃቸውን አጣጥፈው እንዲቀመጡ እያደረገ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ወጣቱ ትራክተር ይዞ መሥራት ይችላል፡፡ ኮሜርሻላይዜሽን በኢትዮጵያውያን ነው መያዝ ያለበት፡፡ ኢትዮጵያዊው ቢያጠፋም እየተማረ አገሩን ያሳድጋል፡፡ የውጭው ባለሀብት ቴክኖሎጂውን ይዞ መጥቶ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ሥርዓት ሳይዘረጋ ገንዘቡን ይዞ ይሄዳል፡፡
በትላልቅ እርሻዎችና በውጭ ባለሀብቶች ላይ ጥናት ባላደርግም ከመገናኛ ብዙኃንና ከአንዳንድ ሰዎች እንደምሰማው የውጭ ባለሀብቶቹ ውጤታማ ሲሆኑ አይስተዋልም፡፡ ለምሳሌ በጋምቤላ አካባቢ የተሰማራ የውጭ ኩባንያ አልተሳካለትም፡፡ በውጭ አገር ያሉ የዘርፉን ባለሙያዎች በመጠቀም ወጣቱን እያስተማርነውና እያገዝነው ቢሰራ የተሻለ ውጤት ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሜካናይዜሽን ዓለም የደረሰበትን ደረጃ ከኢትዮጵያ ጋር በማነፃፀር ቢያብራሩልን?
ዶክተር ጌታቸው፡- በዓለም ያለው የሜካናይዜሽን ደረጃ 12ኛው እርከን ላይ ደርሷል፡፡ 12ኛ እርከን ማለት እጅግ በጣም ከፍተኛ የኮምባይን ሀርቨስተር እና እስከ 300 የፈረስ ጉልበት ያለው ትራክተርን የመጠቀም ደረጃ ነው፡፡ ይህ ትራክተር በአንድ ጊዜ እስከ 500 ሜትር እያረሰ መሄድ ይችላል፡፡ ይሄንን ከዲጂታል ቴክኖሎጂው ጋር በማገናኘት በጥቂት ሰው ብዙ መሳርያ በማንቀሳቀስ፣ ብዙ መሬት ማረስ የሚቻልበት ዘመን ላይ ተደርሷል፡፡ በሌላ አማርኛ ዓለም ቴክኖሎጂውን አሳድጎ በሮቦት ማረስ ተጀምሯል፡፡
ኢትዮጵያ ከአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ብዙም አልዘለለችም፡፡ አንደኛው እርከን በእጅ ማረስና በዶማ መቆፈር ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ በሬ ጠምዶ ማረስ ሲሆን፣ ሦስተኛው ከእርሻ በሬ ጋር በተወሰነ ደረጃ ትራክተር መጠቀም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ጥቂት ሊባል በሚችል መልኩ ባለሁለት እግር አነስተኛ የፈረስ ጉልበት ያለው ትራክተር ከበሬ ጋር ጥቅም ላይ ሲውል ይስተዋላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግብርናውን በማዘመኑ ሂደት ውስጥ ተጠቃሚዎች የመኖራቸውን ያህል የሚጎዱ ዜጎች ይኖራሉ፣ ይህ እንዴት ይጣጣማል?
ዶክተር ጌታቸው፡- ይሄ እውነት ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያመጣው ቀውስ መኖሩ በእነ አሜሪካና ብራዚል ታይቷል፡፡ ግብርና ሲዘምን የሚያሸንፍና የሚሸነፍ ቡድን ይኖራል፡፡ የሚያሸንፈው ቡድን ስጋቱን ወስዶ ቴክኖሎጂውን አላምዶ ወደ ሥርዓቱ ይገባል፡፡ በጣም ጠባብ መሬት ያለው ደግሞ ተሸናፊ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
መሬትን በማሰባሰብ የትራንስፎርሜሽን ሂደት ውስጥ ሊጎዱና ሊጠቀሙ የሚችሉ አካላት መኖራቸውን በማስረዳት ሊጎዳ ለሚችለው ማህበረሰብ የማህበራዊ ደህንነት ዋስትናውን በማረጋገጥ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በዚህ ፍራቻ የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ገፍቶ አልሄደበትም፡፡
በዓለም አገራት ግብርናውን ለማዘመን በተደረገው ሂደት ለተጎዱት ሰዎች ጉዳታቸውን ለማካካስ ነው የተሰራው፡፡ በኢትዮጵያም ለተጎጂዎች የማኅበራዊ ዋስትና አገልግሎት የሚሰጥ ብሔራዊ አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በገጠር ከሚተገበረው የሴፍትኔት፣ እንዲሁም በከተማ ከተጀመረው የምግብ ዋስትና ፕሮግራም እልፍ ብሎ ይህን አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ማቋቋም ይቻላል፡፡
ባንኩ አርሶ አደሮች የሚቆጥቡበት ሲሆን፤ የምርት ችግር ሲገጥማቸው ይህንን ለመቋቋም የሚችሉበትን ቁጠባ የሚያስተናግድ መሆን አለበት፡፡ መቆጠብ ለማይችሉት አነስተኛ አቅም ላላቸው አርሶ አደሮች መንግሥት መዋጮ በማድረግ በባንኩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማገዝ አለበት፡፡ ይህ ዘላቂነት የሌለውን በምግብ አቅርቦትና በዕርዳታ ላይ የተመሰረተውን የማህበረሰብ ድጋፍ ይተካል፡፡ ዕድር፣ ዕቁብና መሰል ማህበረሰባዊ ተቋማትን በማጠናከር ችግሩን መከላከል ይቻላል፡፡
እርሻው እየዘመነና እያደገ ሲሄድ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ወጣቶች ትራክተር ኦፕሬተር፣ አጫጅ፣ አራሚ ሆነው ይቀጠራሉ፡፡ በእህልና ወተት ማከፋፈል ንግድ እና በአገልግሎት ዘርፍ ይሰማራሉ፡፡ በዚህ በኩል በደንብ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባት ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጥናትዎ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችን በተለያየ ደረጃ ከፋፍለው ለማስቀመጥ ሞክረዋል፡፡ ደረጃዎቹንና ምን ያህል አርሶ አደሮች በየደረጃዎቹ እንዳሉ ቢገልፁልን ?
ዶክተር ጌታቸው፡- የኢትዮጵያ አርሶ አደር በአራት ይከፈላል፡፡ አንደኛው በድቀት ውስጥ ያለ ነው፡፡ ይሄ ለመኖር መሰረታዊ የሆነውን ምግብ ማግኘት የማይችል ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ወደ ሠላሳ አምስት ሚሊዮን አርሶ አደር አለ፡፡
በሁለተኛው ደራጃ ውስጥ የሚካተቱት እየተንገታገቱም ቢሆን መኖር የሚችሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ጥሩ ምርት በሚገኝ ወቅት ምግባቸውን መሸፈን የሚችሉ ናቸው፡፡ የጤናና የትምህርት መሰረታዊ ነገሮችን ወጭ መሸፈን ቢችሉም፤ እርሻቸውን አያዘምኑም፤ ቁጠባም የላቸውም፡፡ እነዚህ 55 ሚሊዮን ህዝብ ይሆናሉ፡፡
‹‹ሪኒዋል›› ወይም ጥሩ ማምረት የሚችሉት ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣሉ፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች ምግባቸውን ይችላሉ፤ ዓመታዊ የጤናና የትምህርት ወጭያቸውን ይሸፍናሉ፡፡ ማዳበርያን የመሳሰሉ የእርሻ ግብዓቶችን መግዛት ይችላሉ፡፡
አራተኛው ደረጃ ኢንተርፕራይዝ አርሶ አደሮች ይባላሉ፡፡ እነዚህ ከ200ሺ (አንድ ነጥብ ሁለት በመቶ) የማይበልጡ አርሶ አደሮች ናቸው፡፡ ሀብታም በመሆናቸው ችግር ቢፈጠር መቋቋም ይችላሉ፡፡ ምግባቸውን ይሸፍናሉ፤ እርሻውን ያዘምናሉ፤ ይቆጥባሉ፤ በባንክ ገንዘብ አላቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግብርናውን ለማሳደግ ከማን ምን ይጠበቃል?
ዶክተር ጌታቸው፡- ግብርናን የማሳደግ ኃላፊነት ለፖለቲከኞች ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የሚመለከት ግዴታ ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ሰዎች ቴክኖሎጂው በደንብ እንዲሰርፅ መሥራት አለባቸው፡፡ የሃይማኖት ሰዎች በግብርናው ዘርፍ የሚወጡ አዳዲስ ግኝቶችና ቴክኖሎጂዎችን ጠቀሜታ ለህዝቡ መስበክ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ምሁራን ነባራዊውን አስተሳሰብ ይዘው ከማናፈስ ተሃድሶ የሚያመጡ አዳዲስ ምርምሮችን ማውጣት አለባቸው፡፡ ሲያስተምሩና ሲመራመሩም ይህን ታሳቢ መድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
ፖለቲከኞች የራሳቸውን ችግር የሚቀርፍ ሳይሆን ለትውልድ የሚተላለፍ የፖለቲካ አውታር በመዘርጋት ሕዝብን አንቀሳቅሰው ወደ ዘመናዊ ህይወት የሚያመጣ ሽግግር ውስጥ መግባት አለባቸው፡፡ ለትውልድ ጠቃሚ ታሪክ ሠርቶና ሥርዓት ዘርግቶ ማለፍ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ጌታቸው፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።