ትኩረትን ያጣው ነጭ ወርቅ Featured

09 Jul 2018
በዘንድሮ በጀት ዓመት 128 ሺ ኩንታል ነጭ ቦሎቄ ለገበያ ቀርቧል፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት 128 ሺ ኩንታል ነጭ ቦሎቄ ለገበያ ቀርቧል፤

ገና ከረፋዱ የወጣውና አናት በስቶ የመግባት ሃይል ያለው የፀሃይዋ ሙቀት ከነፋሻማው አየር ጋር ተደማምሮ አንዳች ስሜትን ይፈጥራል፡፡ ምንም እንኳን አናቴ ቁልቁል በሚወርደው ሙቀት፤ ዓይኖቼም በነፋሱ ቢቸገሩም የምጓዘው ወደ አዳማ ከተማ ነውና ስለሷ ከተዜሙ ዘፈኖች መካከል የአንዱን በምስል የተደገፈ ሙዚቃ እያዳመጥኩ፣ እናት የቦለቄ ንፍሮ ጨብጠው ለልጁ ሲያሲዙት ስለሚያሳየው የተንቀሳቃሽ ምስል እያሰላሰልኩ የቦለቄ ምርትን ከሚቀበለው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዳማ ቅርንጫፍ ደረስኩ፡፡
በጊቢው ውስጥ በርካታ ቦለቄ የያዙ ማዳበሪያዎች ላይ በላይ ተደራርበውና ተሽከርካሪዎች ላይ ተጭነው ይታያሉ፡፡ ሜዳው ላይ በተነጠፈ ሸራ የተወሰነው ምርት ፈስሶ ሰራተኞች ስራቸውን ሲሰሩ ተመለከትን፡፡ ይሄኔ ታዲያ ምርቱ በዚህ መልኩ መያዙ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ የለም ይሆን? የሚል ጥያቄን አጫረብን፡፡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የተቸረችና በርካታ ተግባራትንም ለማከናወን መልከዓ ምድራዊ አቀማመጧ ምቹ እንደሆነ ሲገለፅ ቢደመጥም በዚህ ልክ ዕድገት ላለማስመዝገቧ ደግሞ የአፈፃፀም ችግር በሚል ምክንያት ይቀመጣል፡፡ እናም የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ለቦለቄ ምርት አመቺ መሆኑ ታሳቢ ተደርጎ የተቋቋመው ቅርንጫፍም ከዓመት ዓመት ገቢ የሚያደርገው ምርት እያሽቆለቆለ መምጣቱን ተከትሎ ከቅርንጫፉ ኃላፊ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ፡፡
አጠቃላይ ሁኔታ
በ2002 ዓ.ም የተቋቋመው ቅርንጫፉ አራት ድርጅቶች በጋራ በሚጠቀሙበት ቅጥር ግቢ ውስጥ ስራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ሰብል ምርትን ለመቀበል በሚል ስራውን እንደጀመረ የሚገልፁት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዳማ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ጅራታ፤ ቅርንጫፉ ቦለቄ ላይ እንደሚሰራ ይናገራሉ፡፡ ከወረዳዎች ወደ ተቋሙ የገባውን ምርትም ደረጃ የማውጣት፣ ምርቱን ተቀብሎ በማቆያ ማስቀመጥ እንዲሁም የምርቱን መረጃ ለበላይ አካል ለግብይት ማስተላለፍ ስራዎችን ይሰራል፡፡ ምርቱ ሲሸጥም ለገዢው ማስተላለፍ የዚሁ ማዕከል ኃላፊነት ነው፡፡
ወደ ቅርንጫፉ ነጭና ቀይ የቦሎቄ ሰብል ዝርያዎች እንደሚገቡ የሚናገሩት አቶ ዘላለም፤ 95 በመቶ የሚሆነው ስራ ግን ነጭ ቦለቄ ላይ እንደሚሰራ ያስረዳሉ፡፡ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ እንዲሁም ከደቡብ ክልሎች የሚቀርበው ቦለቄ አፈፃፀሙም ካለፉት ዓመታት ጋር በንፅፅር ሲታይ በዘንድሮ በጀት ዓመት የተሻለ ነው፡፡ ምንም እንኳን በአገሪቱ ምርታማነቱን ማሳደግም ሆነ በጥራት የተሻለ አቅርቦት ማግኘት የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ ቢኖርም፤ የተጠናከረ የጋራ አሰራር አለመኖሩና ህገ ወጥነቱ ሸብቦት ወደ ኋላ እየጎተተው ይገኛል፡፡ ይህም ባለው አቅም ልክ እየተሰራ አለመሆኑን ያመላክታል፡፡
ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ያለው የአቅርቦት መጠንም እስከ 2005 ዓ.ም የዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ዋጋ ጥሩ ስለነበር ከ385 ሺህ ኩንታል እስከ 500 ሺህ ኩንታል ደርሶ እንደነበር አቶ ዘላለም ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ቅበላው ከአምስት መጋዘን ወደ አንድ ዝቅ በማለት 56 ሺህ ኩንታል ብቻ አድርጎታል፡፡ በዘንድሮ በጀት ዓመትም ምንም እንኳን በቂ ነው ባይባልም መልሶ ማንሰራራት በማሳየት የመቀበል አቅሙ ወደ 128 ሺህ ኩንታል ማድረግ ተችሏል፡፡
ችግሮች
በኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዳማ ቅርንጫፍ የጥራት ሱፐርቫይዘር አቶ አወቀ አቅናው ገለጻ፤ በዘርፉ የቅንጅት ጉድለት በመኖሩ 39 በመቶ ያክል ለዓለም ገበያ የማይውል ምርት እንዲገበያይ ይፈቅዳል፡፡ ላኪዎችም በመውሰድ ጥራቱን እንዲጠብቅ አድርገው ለውጭ ገበያ ያቀርቡታል፡፡ ይህ ደግሞ በአንድም በሌላ መልኩ ገቢ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ አለ፡፡ ገበያ የተለያዩ አካላት ተሣትፎ ውጤት ቢሆንም ይህን ተገንዝቦ ቅንጅታዊ ስራ መስራት ላይ ግን ክፍተት ይታያል፡፡
በዚህም ያለፉት ሶስት ዓመታት መረጃ እንደሚያሳየው ከቀረበው ምርት 47 በመቶ ደረጃውን ባለማሟላቱ ጥራቱን ጠብቆ እንዲመጣ ተመላሽ ተደርጓል፡፡ ይህም የተለያዩ አካላት ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ በቅንጅት እየሰሩት ያለው ስራ ክፍተት እንዳለበት አመላካች ነው፡፡
እንደ አቶ አወቀ ገለፃ፤ የስራው ክፍተት በምርምር ማዕከል ምርጥ ዘር ከማቅረብ ይጀምራል፡፡ ከአርሶ አደሩ የማሣ ዝግጅት ጀምሮም ለውጭ ገበያ ቀርቦ ገቢ እስኪያመጣ ያለው ሂደት በጥንቃቄና በቅንጅት ካልተሰራ በአሁኑ ወቅት ቦለቄ ከአገሪቱ እጅ እየወጣ ነው፡፡
በዋናነት በዘርፉ ከሚስተዋሉት ችግሮች መካከል አንዱ የግንዛቤ ማጣት ነው፡፡ ይሄም አምራች፣ አቅራቢና የባለድርሻ አካላት ጋር ከታችኛው እስከ ላይኛው መዋቅር ተቀናጅቶ ያለመሰራቱ ዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ ውጤት እንዳያመጣ እያደረጉት ከሚገኙት ምክንያቶች ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከ2005 ዓ.ም በኋላም ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ያሽቆለቆለ ሲሆን ለዚህም እንደ ምክንያት የሚነሳው የዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ዋጋ ነው፡፡
በዚሁ ችግር ላይ ተደማምሮም ህገወጥነት መስፋፋቱ ጥቂቶችን በማክበር በአገር ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ የትየለሌ እንደነበር ሥራ አስኪያጁ ያስታውሳሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ከታች ጀምሮ ያለው አሰራርና ቁጥጥር መላላቱ ከአምራች ጀምሮ እስከ አገር ጉዳት አድርሷል፡፡ በርካቶችም ከማረት እንዲወጡ አድርጓቸዋል፡፡ ከ2009 ዓ.ም በኋላም የዋጋ መነቃቃት በመፈጠሩ በተያዘው በጀት ዓመት የማንሰራራት ሁኔታ እየታየ ይገኛል፡፡
ምክረ ሀሳብ
መስሪያ ቤቱ ከብልሹ አሰራር ጋር ተያይዞ የሚነሱበት ችግሮች እንደነበሩ የሚያወሱት ሱፐርቫይዘሩ፤ ይህን ተከትሎ ባለፉት ሶስት ዓመታት ትልልቅ ቅሬታዎችን በማስተናገዱ ሁለት የለውጥ እርምጃዎችን አድርጓል፡፡ ትልቅ ማዕበል ውስጥ እንዳለ የሚያመላክቱም ችግሮች በመኖራቸው ተቋሙ ራሱን መፈተሸ እንዳለበት በማንሳት ባለሙያውም በብልሹ አሰራር ውስጥ የተዘፈቁ ካሉ መታገልና የጋራ ስራ መስራት ይገባል ባይ ናቸው፡፡ ዘርፉ ለአገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን ትልቅ አስተዋፅዖ በመገንዘብ ሁሉም የራሱን ድርሻ ሊወጣ የሚያስችለው ስራ መከናወን ይኖርበታል፡፡
ምርቱ በድንበር አካባቢ የሚመረት ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነው በህገወጥ ንግድ ከአገር ይወጣል፡፡ ይህም የአገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ከመጉዳቱ ባሻገር የምርት ጥራት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ አስተዋፅዖም ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ለዚህም ቀጣይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ላይ ማተኮር የማይተካ ሚና አለው የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ተቀናጅቶ በመስራት በህገወጥ መንገድ የሚወጣውን ምርት መቆጣጠር በተያያዥነት ሊሰራ እንደሚገባ ያመላክታሉ፡፡ በመሆኑም በዚህ ተግባር ላይ ተሣታፊ የሆኑ አካላትን ወደ ህጋዊነት ማሸጋገር ተገቢ ይሆናል፡፡ ጎን ለጎንም የሚጠበቅበትን ተግባር ያላከናወነም ተጠያቂ ሊደረግ ይገባል፡፡
በተለያዩ ችግሮች የታሰረው ይህ ዘርፍ ሰፊ ስራ ቢሰራም በቂ አገልግሎት መስጫ እንኳ እንደሌለው ሥራ አስኪያጁ ይጠቁማሉ፡፡ ድርጅቱ ከ325 በላይ ነጋዴዎችን፣ የአገልግሎት ህብረት ስራ ማህበራት፣ እንዲሁም በግል አምርተው የሚያቀርቡትን የሚያገለግል ነው፡፡ ይሁን እንጂ የራሱ የሆነ ቢሮና መጋዘን እንዲሁም ሚዛን የለውም፡፡ በመሆኑም የተሰሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት እነዚህ ጉዳዮች በተጓዳኝነት ሊታዩ ይገባል፡፡
ቀጣይ አቅጣጫዎች
ባለሀብቶች ምርትን በጥሬው ከመላክ ይልቅ ዕሴት መጨመር ላይ የሚያተኩሩበት ሁኔታ ቢመቻች የተሻለ ገቢን መፍጠር እንደሚቻል አቶ አወቀ ይገልፃሉ፡፡ በሌላ በኩል ከተቋሙ ጋር መስራት ያለባቸው አካላት ባለስልጣኑን ጨምሮ በሚፈለገው ደረጃ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ በዚህም በህገወጥ መንገድ የሚወጡ ምርቶች ወደ ተቋሙ እንዲገቡ ማድረግ ላይ ትኩረት መሰጠት ይኖርበታል፡፡
ትልቁ የትኩረት አቅጣጫ ከምርት ገበያ ባለስልጣን ጋር በመቀናጀትም የግንዛቤ ስራውን ማሳደግ ይሆናል፡፡ ይህም ከታች እስከ ላይ ያለውን ሂደት አጠናክሮ በማስቀጠል የጋራ ቁጥጥር ሥርዓቱን ለማሳለጥ ያስችላል በማለት በቀጣይ የሚሰሩት ስራዎች ዘርፉን ለማሳደግ የሚኖራቸውን ቀላል የማይባል ድጋፍ ሥራ አስኪያጁ ያመላክታሉ፡፡

ፍዮሪ ተወልደ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።