ፋብሪካዎችንና ሸማቹን የፈተነው የስንዴ እጥረት

12 Jul 2018

ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ያጋጠመውን የዳቦ ስንዴ ዱቄት እጥረት ለመፍታት መንግስት እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡ገበያን የማረጋጋት ኃላፊነት ያነገበውና በንግድ ሚኒስቴር ስር የሚገኘው የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ከብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የስንዴ ክምችት የዳቦ ስንዴ በመውሰድ የተፈጠረውን እጥረት ለመቅረፍ ለዱቄት አምራቾች በዝቅተኛ ዋጋ ለማቅረብ ተገዷል፡፡
በዚህም የተከሰተውን የዳቦ እጥረት ችግር በመጠኑ ለማስታገስ ቢቻልም አሁንም የዳቦ አቅርቦት ቤቶች አልተቀረፈም፡፡ ወረፋው አልቀረም፡፡ የዳቦ መጠን መቀነሱን ሸማቾች ይናገራሉ፡፡ ችግሩ በአዲስ አበባ በስፋት ይስተዋላል፡፡ በክልል ከተሞችም መሰል ችግሮች መከሰታቸውን ነዋሪዎቹ ያስረዳሉ፡፡
የሶስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ መሰረት መንግስቱ በአዳማ ከተማ በተለምዶ ዮሐንስ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ ዳቦ የቤተሰባቸው የእለት ተእለት ምግብ ነው፡፡ ከሚያዝያ ወር ወዲህ ዳቦ ማግኘት አዳጋች ሆኖ መቆየቱን ያነሳሉ፡፡ በብዙ ልፋት ከተማዋ ውስጥ ዳቦ ቢገኝ እንኳን ለማግኘት ረጅም ወረፋ መጠበቅ ግድ ነው፡፡ የዳቦ መጠን መቀነሱን ያወሱት ወይዘሮ መሰረት ከሁለት ወራት ወዲህ ያጋጠመው የዳቦ እጥረት በኑሯቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉን ያነሳሉ፡፡ ዳቦ ለማግኘት ሰዓታት ወረፋ ከመጠበቅ ጀምሮ ከሌሊቱ 10 ሰዓት የዳቦ ወረፋ ለመያዝ የወጡበት ቀን እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ወረፋ መጠበቁ የሰለቻቸው ወይዘሮ መሰረት ለተወሰኑ ጊዜያት ከዳቦ ቤቶች የሚገዛውን ዳቦ በመተው ስንዴ ገዝተው አስፈጭተው ራሳቸው ዳቦ እየደፉ ሲጠቀሙ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ሳምንት በዳቦ ቤቶች አካባቢ የሰልፉ ወረፋ ስለቀነሰ ዳቦ ቤት ለመግዛት የመጡ ሲሆን ሆኖም የዳቦው መጠን መቀነሱን ተናግረዋል፡፡
የዳቦ ዱቄትና ዳቦ በማምረት የታወቀው የሸዋ ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ የአዳማ ቅርንጫፍ ስራ አሥኪያጅ አቶ ፍስኃ ነጋ ከዚህ ቀደም ለዳቦ ዱቄት የሚሆን ስንዴ ከመንግስት በዝቅተኛ ዋጋ ይቀርብ የነበረ ሲሆን ድርጅቱም ለሸማቹ ዳቦ በዝቅተኛ ዋጋ ሲያቀርብ ኖሯል፡፡ ከሚያዚያ 2010 ዓ.ም ወዲህ የዳቦ ስንዴ እጥረት በማጋጠሙ ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው ዳቦና ዱቄት ለማምረት አለመቻላቸውን ይናገራሉ፡፡ ከአዳማ ውጭ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የፋብሪካው ቅርንጫፎችም የአቅማቸውን ያህል እያመረቱ አይደለም፡፡
ከመንግስት እየቀረበ የነበረው የስንዴ ኮታ ከሁለት ወራት ወዲህ ቀንሶአል፡፡ ስንዴ በጊዜ እየቀረበ አለመሆኑን ያነሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በቀን እስከ 450 ኩንታል የዳቦ ዱቄት የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት በቀን 300 ኩንታል ብቻ ለማምረት ተገዷል፡፡ ማምረት ከነበረበት 150 ኩንታል ቀንሷል፡፡ በዚህም ምክንያት ድርጅቱ ለዳቦ ፈላጊው ሕብረተሰብ በበቂ ደረጃ ማቅረብ አልቻለም፡፡ ሕዝቡ ከሌሊቱ 9፡00 ጀምሮ ወረፋ የሚጠብቅበት ጊዜ መኖሩንም ይናገራሉ፡፡
አቶ ፍስኃ እንደሚያብራሩት፤ አንዳንድ ወቅት ለፋብሪካው መቅረብ ካለበት ድርሻ ከግማሽ በታች የሚቀርብ ሲሆን በሌላ ጊዜ ደግሞ በጣም ዘግይቶ መቅረቡ ሸማቾች በዳቦ እጥረት እንዲቸገሩ ከማድረጉም በላይ ፋብሪካው ስራ ሳይሰሩ ለሰራተኞቹ ደሞዝ እየከፈለ አስፈላጊ ላልሆነ ወጪ ተዳርጓል፡፡ የሚቀርበውን ውስን ስንዴ እየቆጠበ ምርቱ እንዳይቋረጥ እስካሁን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህ መልኩ የስንዴ አቅርቦት ችግር የሚቀጥል ከሆነ ፋብሪካው ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ምርቱን ያቆማል፡፡
ኃላፊው በግንቦት ወር የቀረበውን ጥቂት ስንዴ በቁጠባ በመጠቀም እስካሁን ድረስ ፋብሪካው ዱቄትና ዳቦ እያመረተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡በአንድ ጊዜ አልቆ ድርጅቱ እንዳይዘጋ በጥንቃቄ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ፋብሪካው በሙሉ ኃይሉ እየሰራ ባለመሆኑ ትርፋማነቱ ላይ የራሱን አሻራ አሳርፎአል፡፡
በስንዴ እጥረቱ ምክንያት እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመፍታት ለመንግስት ሪፖርት ማድረጋቸውን ለንግድ ሚኒስቴር ተደጋጋሚ ደብዳቤ መጻፉን ጭምር ገልጸዋል፡፡ የሚቀርበው ስንዴ በቂ አለመሆኑን በጊዜ እየቀረበ እንዳልሆነ ለንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የአዳማ ቅርንጫፍና ለዋናው የአዲስ አበባ ቢሮ አመልክተዋል፡፡
መንግስት የስንዴ አቅርቦት ችግርን ከፈታ ፋብሪካው መብራት ቢቋረጥ እንኳን ጄኔሬተር በመጠቀም 24 ሰዓት በመስራት ከዚህ ቀደም ለሸማቹ ዳቦ ለማቅረብ ያደርግ የነበረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በስንዴ አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች የሚቀረፉ ከሆነ ድርጅቱ ቅርንጫፎችን የማስፋፋት እቅድ እንዳለው ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
በቢሾፍቱ የሚገኘው አዋሽ ዱቄትና ብስኩት ፋብሪካ ተወካይ አቶ ደሳለኝ በቀለ በበኩላቸው፤ ፋብሪካቸው ለንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ቅድመ ክፍያ የፈጸመ ቢሆንም ኮርፖሬሽኑ የስንዴ እጥረት ስላለበት ስንዴን ማቅረብ አለመቻሉን ያነሳሉ፡፡ ከግንቦት ወር እስከ ሰኔ ማብቂያ አንድ መኪና ብቻ ስንዴ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ስንዴ በወቅቱ ባለመቅረቡ በቢሾፍቱ ነዋሪ ብሎም በፋብሪካው ላይ አደጋ ተደቅኗል፡፡ በከተማዋ በርካታ የዳቦ ዱቄት የሚፈልጉ ዳቦ ቤቶችና ሸማቾች አሉ፡፡ ፋብሪካው በዳቦ እጥረት ሳቢያ ፍላጎታቸውን ማሟላት አልቻለም ብለዋል፡፡
ኃላፊው በስንዴ እጥረት ምክንያት በግንቦት ወር ለፋብሪካው መቅረብ ከነበረበት ኮታ አንድ አራተኛ ብቻ እንደቀረበ ይናገራሉ፡፡ ከሰኔ ወር ጀምሮ ምንም ሊቀርብ አልቻለም፡፡ ለአንድ ወር ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ስራውን አቁሟል፡፡ ሆኖም ያለስራ ያለምርት ለሰራተኞች ደሞዝ ይከፍላል፡፡ በዚህም ፋብሪካው ለጉዳት እየተዳረገ መሆኑን አቶ ደሳለኝ ይገልጻሉ፡፡
በቅርቡ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ከጅቡቲ ካስመጣው ስንዴ ውስጥ 400 ኩንታል የደረሳቸው መሆኑን የሚናገሩት አቶ ደሳለኝ፤ ፋብሪካቸው ይህን ስንዴ ፈጭቶ ዳቦና ዱቄት ለሸማቹ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም አቅርቦቱና ስርጭቱ ባለመመጣጠኑ የተነሳ የከተማዋን ፍላጎት እንደማያሟላ ይገልጻሉ፡፡ በከተማዋ ያሉት ሌሎች ዱቄት አምራች ፋብሪካዎች በስንዴ እጥረት ሳቢያ ዱቄትና ዳቦ ማምረት ማቆማቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በወላይታ ሶዶ የአወል ሸረፈዲን ዱቄት ፋብሪካ የምርትና ቴክኒክ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ እንዳሻው ኃይሌ በበኩላቸው ከጅቡቲ የሚመጣውን ስንዴ በመጠባበቅ በአዳማ ከተማ ከ50 ቀን በላይ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡ ወላይታ ሶዶ ደርሰው እንዳይመለሱ ከዛሬ ነገ ወረፋ ደርሶ ስንዴ እወስዳለሁ በሚል ተስፋ በመጠባበቅ ራሳቸውንና ፋብሪካውን አስፈላጊ ላልሆነ ወጪ እየዳረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው ስራ ማቆሙን የሚናገሩት አቶ እንደሻው ስንዴ ከዛሬ ነገ ይመጣል በሚል ተስፋ ለሠራተኞቹ ደሞዝ እየከፈለ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በሆሳዕና ከተማ የሚገኘው የሀዲያ ሊቻ ዱቄት ፋብሪካ ተወካይ አቶ ተስፋዬ ሱለንቆ፤ ፋብሪካው በሆሳእና ከተማ ላሉት ዳቦ ቤቶች ዱቄት ከመሸጥ ባሻገር በዞኑ ለሚገኙ ወረዳዎችም የዳቦ ስንዴ ያቀርባል፡፡ከቅርብ ወራት ወዲህ በተከሰተው የስንዴ እጥረት የተነሳ ፋብሪካው የሚጠበቅበትን ማምረት አልቻለም፡፡ከግንቦት ወር ወዲህ አንዴ ብቻ ከመንግስት ስንዴ እንደወሰዱ ይናገራሉ፡፡ ከግንቦት 12/2010 ጀምሮ ከሆሳእና አዳማ ከተማ በመመላለስ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡በግንቦት ወር ለፋብሪካው በቂ ኮታ አልወሰዱም፡፡የሰኔ ወር ኮታ በተባለበት ቀን አዳማ ሊደርስ ባለመቻሉ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
ሀዲያ ዞን ስንዴ በስፋት ይመረትበታል፡፡ከፍተኛ የስንዴ ክምችት አለ፡፡መንግስት ከሚያቀርበው ዋጋ ጋር ከፍተኛ ልዩነት ስላለው የአካባቢውን ስንዴ ገዝቶ ለመጠቀም አልተቻለም፡፡የአካባቢው ስንዴ መቶ ኪሎ 1400 እየተሸጠ መንግስት የሚያቀርበው ግን 500 ብር ነው የሚሸጠው፡፡
በንግድ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ፍላቴ እንደሚሉት በተያዘው በጀት ዓመት የትራንስፖርት፣ የአውራጅ፣ የጫኝ፣የማሸግና ሌሎች ወጪዎችን መንግስት ሸፍኖ ለስንዴ ዱቄት አምራች ፋብሪካዎች ሰባት ነጥብ 12 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማቅረብ አቅዶ ነበር፡፡ ከሰባት ነጥብ 12 ሚሊዮን ኩንታል ውስጥ አራት ሚሊዮኑን ከውጭ የማስገባት እቅድ ነበረው፡፡ ከውጭ የሚገባው የአራት ሚሊዮን ኩንታል የግዢ ሂደት እስከ ታሕሳስ ማለቅ ነበረበት፡፡ አራት ሚሊየን ኩንታል የዳቦ ስንዴ ተገዝቶ እንዲገባ የፌዴራል ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ለፌዴራል ግዥ ኤጀንሲ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ስፔስፊኬሽንና ጨረታ ወጥቶ የግዢ ሂደት ላይ በነበረበት ሁኔታ ላይ ተጫራቾች ማሟላት ያለባቸውን መስፈርት ማሟላት ባለመቻላቸው ሁለት ጊዜ ጨረታው ውድቅ ተደርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት መግባት የነበረበት ስንዴ ሀገር ቤት ሳይገባ ቀርቷል፡፡ እስከ መጋቢት ድረስ ስንዴ ሀገር ቤት ባለመግባቱ የተነሳ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ የስንዴ አቅርቦት እጥረት ተከስቷል፡፡ በዚያም ምክንያት የዳቦ እጥረት መከሰቱን ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
አቶ ወንድሙ የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የእህል ክምችት ስንዴ በመውሰድ ለዱቄት አምራቾች እንዲቀርብ መደረጉን ይናገራሉ፡፡ ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ በሚደረገው ጉዞ ላይ በተፈጠረው የትራንስፖርት መጓተት ምክንያት ለፋብሪካዎች በወቅቱ ለማቅረብ አለመቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ከውጭ የገዛው አራት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ወደ ሀገር ቤት በመግባት ላይ ይገኛል፡፡ ከአራት ሚሊዮን ኩንታል ውስጥ ሁለት ሚሊዮን ተገዝቶ በአሁኑ ወቅት ሀገር ውስጥ ገብቶአል፡፡ ከዚህ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ጭነቶች ከጅቡቲ ኢትዮጵያ ገብተው በየአካባቢው ለሚገኙ ዱቄት አምራች ፋብሪካዎች በመከፋፈል ላይ ናቸው፡፡ በሁለተኛ ዙር ለሚገባው ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ደግሞ ጨረታ ወጥቶ አሸናፊ ተለይቶ ውል መፈጸሙን ነው ያብራሩት፡፡
ወቅቱ የመኸር ወቅት ስለሆነ ከፍተኛ ማዳበሪያ ከውጭ የሚገባበት ነው፡፡ ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የሚጓጓዝ ማዳበሪያ ቅድሚያ እንዲሰጠው በመወሰኑ የተነሳ ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የትራንስፖርት ችግር መፈጠሩን አንስተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ማዳበሪያ የማጓጓዝ ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑን፤ከአሁን በኋላ ስንዴን የማጓጓዙ ስራ በትኩረት እንደሚሰራ፤ በዚህም መሰረት የዱቄት አምራቾችንና የዳቦ ሸማቹን ችግር ለመቅረፍ ጥረት እንደሚደረግ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ በቅርቡ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት መልስ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃ እጥረትን አስመልከቶ በሰጡት ምላሽ ስንዴን ጨምሮ በተለያዩ የፍጆታ እቃዎች ላይ ለሚስተዋለው እጥረት ምክንያቱ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
ለዚህም ስንዴን የመሳሰሉ የምግብ ምርቶች በሀገር በብዛት ማምረት እንደሚያስፈልግ ነው ያብራሩት፡፡ የዜጎችን የመግዛት አቅም ማሳደግ እንደሚገባ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

መላኩ ኤሮሴ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።