Items filtered by date: Sunday, 01 October 2017

የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ለ2010 .ም ስራ ማስኬጃ የሚሆነውን አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በጀት ማፅደቁን አስታወቀ፡፡ ፌዴሬሽኑ 18ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ ሲያካሂድ፤ ባለፈው ዓመት የተፈጠሩትን አለመግባባቶች በበርካታ ውይይቶች በመፍታት ስፖርቱን ለማስፋፋት ያደረገው እንቅስቃሴ ቢያበረታታም ዘንድሮ በተሻለ መልኩ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

በጉባዔውም እንደተገለጸው በወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር አማካኝነት የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ለበርካታ ወራት ቢዘጋም በስራ አስፈጻሚ አባላቱ ብርታት ስፖርቱን ለማሳደግ የተደረገው ጥረት በጠቅላላ ጉባዔ አባላቱ ተደንቋል፡፡ በጠቅላላ ጉባዔ ላይ ፌዴሬሽኑ የክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን የአማራ እና ትግራይ ክልል አፈጻጸም በጠንካራነቱ ተጠቅሷል፡፡ በተለይም አማራ ክልል በርካታ የታዳጊ ፕሮጀክት የስልጠና ጣቢያዎችን በማቋቋም ውሃ ስፖርት እንዲስፋፋ ያደረገው ጥረት በአርአያነት ተነስቷል፡፡

የእለቱ ጠቅላላ ጉባዔ በበርካታ አጀንዳዎች ላይ ምክክር አድርጓል፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኪሮስ ሀብቴ በራሳቸው ሙሉ ወጪ በአዳማ ከተማ ያስገነቡት ዘመናዊ የውሃ መዋኛ ገንዳ ይፋ መደረግ አንዱ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ ባለፈው ዓመት በአዳማ ከተማ ለ15 አሰልጣኞች እና ለ15 ዳኞች የሁለተኛ ደረጃ ስልጠና መስጠቱም ተወስቷል፡፡ በተጨማሪም ለ34 ሕይወት አድን ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቶ ወደ ስራ ማሰማራቱ እና የኢትዮጵያ ሻምፒዮናን ለማስተናገድ ተደጋጋሚ ጥረት ማድረጉ ከባለፈው ዓመት አፈጻጸሙ ውስጥ ጠቅላላ ጉባዔው በጠንካራነቱ ያነሳቸው አፈጻጸሞች ናቸው፡፡

ጠቅላላ ጉባዔው ከፌዴሬሽኑ የባለፈው ዓመት የስራ አፈጻጸም ባሻገር የ2010 .ም የስራ እቅድም ሰምቶ ውይይት በማድረግ አጽድቋል፡፡ በስራ እቅዱ ውስጥ ክለቦችን ማቋቋም፣ በርካታ የውድድር እድሎችን መፍጠር፣ ለተለያዩ የስፖርቱ ባለሙያዎች የሙያ ማሻሻያ ስልጠናዎችን መስጠት፣ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ስልቶችን በመንደፍ ፌዴሬሽኑ ከሚኒስቴሩ ድጎማ የሚላቀቅበትን መንገድ መቀየስ፣ የክለቦች ውድድር ማዘጋጀት እና በመላ ሀገሪቱ ያሉ የውሃ ስፖርት የፕሮጀክት ጣቢያዎችን መከታተል እና መደገፍ ላይ በሀገር ውስጥ በተለየ ትኩረት እንደሚሰራ አስቀምጧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከአህጉር ዓቀፍና ዓለም ዓቀፍ ፌዴሬሽኖች ጋር ጠንካራ ግንኙነት በማድረግ የቁሳቁስ እና የስልጠና ድጋፍ ማግኘት እንዲሁም በአፍሪካ የወጣቶች ሻምፒዮና እና የዓለም ሻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ ጥረት ማድረግ በዚህ ዓመት የስራ እቅዱ ውስጥ መያዙን ጠቅሶ በጉባዔው አባላት የማጠናከሪያ ሀሳብ ተሰንዝሮ ጸድቋል፡፡

ጠቅላላ ጉባዔው በመጨረሻ አጀንዳው ፌዴሬሽኑ ካሉት ሰባት የስራ አስፈጻሚዎች ውስጥ የተጓደሉ ሶስት ስራ አስፈጻሚዎችን ለመተካት በተደረገው ምርጫ የቀረቡ ሁለት አዳዲስ የስራ አስፈጻሚ እጩዎችን ተመልክቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡ የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ከተለያዩ ሀገራት ትምህርት እና ስልጠና ለማግኘት እየተጻጻፈ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አቶ ኪሮስ ሀብቴ ይገልጻሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ጽሕህፈት ቤታቸው በመታሸጉ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረግ ባይችሉም ክልሎች ግን ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ፕሬዚዳንቱ አቶ ኪሮስ ተናግረዋል፡፡

«የሚሰራ ሰው ሁልጊዜም ይሳሳታል፡፡ የተፈጠረ ስህተት ካለ እንኳ መነጋገር እና መወያየት እንጂ ቢሮ ማሸግ ተገቢ አይደለም» የሚሉት ፕሬዚዳንቱ አቶ ኪሮስ፣ የቢሯቸው መታሸግ ሳያሳስባቸው ባልተሟላ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ትናንት በተካሄደው የስራ አስፈጻሚዎች የማሟያ ምርጫ የመጡ አዳዲስ የስራ አስፈጻሚ አባላትን በመያዝ በቀጣይ በየክልሉ ተዟዙረው ስፖርቱ በሚያድግበት እና የታዳጊ ፕሮጀክት የስልጠና ጣቢያዎች ያሉበትን ቁመና ለመገምገም እቅድ እንዳላቸውም ፕሬዚዳንቱ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልጸዋል፡፡

2010 .ም የመላ ኢትዮጵያ ውድድር፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስፖርት ውድድር እና ሀገር ዓቀፍ የታዳጊ ፕሮጀክት የምዘና ውድድር እንደሚካሄድ ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ በውሃ ስፖርት ውድድሮች ከመካፈል ባሻገር የኢትዮጵያ ሻምፒዮናን ለማካሄድ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መመረጡንም ጠቁመዋል፡፡ «የውሃ ስፖርት ውድድር ለማዘጋጀት ያለው የማዘውተሪያ ስፍራ ችግር ከባድ ቢሆንም እኔ አዳማ ላይ ዘመናዊ ገንዳ አስገንብቻለሁ፡፡ አቅሙ ካለ በየወሩ ሁሉ ውድድር ማድረግ ይቻላል» የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና በተለያዩ ውድድሮች ላይ ምርጥ ብቃት ያሳዩ ስፖርተኞችን በመምረጥ በዓለም ሻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ ሰፊ ዝግጅት እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡

በጉባዔው ላይ ከአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ጋምቤላ፣ አፋር ፣ ኢትዮ-ሱማሌ ክልሎች እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

 

ታምራት አበራ

Published in ስፖርት

 

አሰልጣኝ ጀስ ማርክት                          የስልጠናው ተካፋዮች በከፊል

 

ለበርካታ ዓመታት አካል ጉዳተኛ መሆናቸው ብቻ ገድቧቸው በስፖርቱ ዘርፍ እንኳንስ መሳተፍ ቀርቶ በተመልካችነቱም ቢሆን በማዘውተሪያ ስፍራ አካባቢ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች አልነበሩም፡፡ በርካታ አካል ጉዳተኛ ዜጎች አቅም አጥተው ሳይሆን በማህበረሰቡ ዘንድ ባለው የተሳሳተ አመለካከት በስፖርቱ ዘርፍ ከሚገኘው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖሊቲካዊ ጥቅም ተቋዳሽ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ጉልህ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በአገሪቱ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የአካል ጉዳተኞች አጀንዳው ዋናው ከሆነ ጥቂት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አካል ጉዳተኞችን በማህበራዊ ጉዳይ ተሳታፊ ለማድረግ እንዲያመች በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት ለመቀየር በርካታ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ በዚህ በኩል ደግሞ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚታይበት ስፖርትን መጥቀስ በቂ ማሳያ ነው፡፡

ቀደም ሲል የነበረው የተሳሳተ አመለካከት ተቀርፎ አካል ጉዳተኞች ከተመልካችነት በዘለለ በስፖርት ተሳታፊነትም ብቅ ብቅ ማለት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ እንኳንስ ለተወዳዳሪነት ለተመል ካችነት ያልታደሉት የቀድሞ አካል ጉዳተኞች እንዳለባቸው የጉዳት ዓይነት በበርካታ የስፖርት ዓይነቶች እየተሳተፉ ሜዳሊያዎችን ማጥለቅ፣ የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብም ችለዋል፡፡

እኤአ መስከረም 22 ቀን 1989 የተመሰረተው እና መቀመጫውን ጀርመን ቦን ከተማ ያደረገው የዓለም ዓቀፉ ፓራሊምፒክ መቋቋም ለአካል ጉዳተኞች የስፖርት ተሳትፎ ከፍተኛ መነሳሳትን ፈጥሯል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት የዚህ ተቋም አባል መሆን የሚያስችላቸውን ስራዎች መስራቱን ገፍተውበት የአባል ሀገራት ቁጥር 176 ደርሷል፡፡

ኮሚቴው በአባላት ሀገራቱ መካከል ውድድርን ለመፍጠር በየአራት ዓመቱ የኦሊምፒክ ውድድርን ተከትሎ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ውድድሮችን እያካሄደ ይገኛል፡፡ ውድድሩ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ መካሄድ ከጀመረ ወዲህ በየሀገራቱ በርካታ ውጤታማ አካል ጉዳተኛ ስፖርተኞችን መመልከት ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያም ባለፉት ሶስት የፓራሊምፒክ ዓለም ዓቀፍ ውድድሮች ላይ በሩጫ ብቻ ተሳትፋለች፡፡ ከቤጂንጉ ኦሊምፒክ ጨምሮ በለንደን እና በሪዮ ኦሊምፒክ ላይ በተለያዩ ጉዳቶች በተወሰኑ አትሌቶች ሩጫን ሞክራዋለች፡፡ የተወሰኑ ሜዳሊያዎችንም ማግኘት ችላለች፡፡ በፓራሊምፒክ ስፖርት ዘርፍ በትኩረት ከተሰራ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻልም ፍንጭ የሰጠ ሆኗል፡፡

በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው የፓራሊምፒክ ውድድሩ በበርካታ የስፖርት ዓይነቶች ውድድሮችን ቢያካሂድም ኢትዮጵያ በሩጫው ብቻ መሳተፏ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽንን አሳሰበው፡፡ ከሶስት ዓመት በኋላ በጃፓን አስተናጋጅነት በሚካሄደው 32ኛው የ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ በዊልቼር ቅርጫት ኳስ ለመሳተፍ እቅድ ይዞ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ከኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

አካል ጉዳተኞች ከሌላው ህብረተሰብ ተገቢው ድጋፍ እና ክትትል ከተደረገላቸው በስፖርቱ ዘርፍ ተሳትፈው አመርቂ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ጽኑ እምነት ያለው ቅርጫት ኳስ ሰሞኑን ከመላ ኢትዮጵያ ለተውጣጡ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ባለሙያዎች ኢንተርናሽናል ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመተባበር ባዘጋጁት በዚህ ኢንተርናሽናል የዊልቸር ቅርጫት ኳስ አሰልጣኝነት፣ ዳኝነት እና የጉዳት መዳቢ (ክላሲፋየር) ስልጠና ላይ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ከ60 በላይ የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ባለሙያዎች እየተሳተፉ መሆኑን ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ከትናንት በስቲያ መስከረም 19 ቀን 2010.ም ጀምሮ እየተሰጠ ያለውን ኢንተርናሽናል ስልጠና ከአሜሪካ የመጡት የአካል ጉዳተኞች ስፖርት አማካሪ ሚስተር ጀስ ማክርት እየሰጡት ይገኛሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ ለሶስት ቀን በንድፈ ሀሳብ የተደገፈ ስልጠና ከሰጠ በኋላ በሀገሪቱ የሚገኙ የተወሰኑ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ተጨዋቾችን በመሰብሰብ ስልጠና እየወሰዱ ያሉ አሰልጣኞችን እና ዳኞችን በውድድር ለመፈተን እቅድ እንዳለውም ታውቋል፡፡

ጀስ ማርክት የዓለም ዓቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የአካል ጉዳተኞች ስፖርት ዘርፍ አማካሪ ናቸው፡፡ ለዊልቸር ቅርጫት ኳስ ባለሙያዎች ስልጠናውን እየሰጡ የሚገኙት ማርክት ባለፉት ስድስት ዓመታት በተለያዩ ሀገራት እየተዟዟሩ ለበርካታ የአካል ጉዳተኛ ስፖርተኞች ስልጠና እና ምክር መስጠታቸውን ገልጸው፣ የአካል ጉዳተኞች የስፖርት ተሳትፎ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን ይገልጻሉ፡፡

አካል ጉዳተኞች የተለየ ትኩረት ቢሰጣቸው በተሰማሩበት የሙያ መስክ ሁሉ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ የጠቀሱት አሰልጣኙ፣ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን አመለካከት ችግር ለመቅረፍ እና የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ስፖርትን ለማሳደግ ተከታታይነት ያላቸው ስልጠናዎች ሊሰጡ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

«አካል ጉዳተኞች የቅርብ አማካሪ ያስፈልጋቸዋል» የሚሉት ሚስተር ማርክት፣ እየሰጡ ባለው ስልጠና ላይ ሰልጣኞቹ ዋና ዋና የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ቴክኒኮችን እንዲቀስሙ እንደሚረዳቸው ገልጸዋል፡፡ በአስር ቀን የኢትዮጵያ ቆይታቸው አራት ቀን ለዳኞች፣ ለአሰልጣኞች እና ለክላሲፋየሮች በንድፈ ሀሳብ የተደገፈ ስልጠና እንደሚሰጡም ተናግረዋል፡፡ ቀሪዎቹን ስድስት ቀናት ደግሞ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ተጨዋቾችን በመሰብሰብ ዋና ዋና የዊልቼር ቅርጫት ኳስ አጨዋወት ቴክኒኮችን በተመለከተ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እቅድ እንዳላቸው ጀስ ማርክት በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡

የዓለም ዓቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በተለየ መልኩ ለዊልቼር ቅርጫት ኳስ እድገት ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ማርክት፣ ኢትዮጵያም ይህንን እድል ተጠቅማ የዊልቼር ቅርጫት ኳስን ለማስፋፋት የስልጠና ፕሮግራም ማዘጋጀቷን አድንቀዋል፡፡ በቀጣይ ኮሚቴው ከኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በሚኖረው ተከታታይነት ያለው ግንኙነት የቁሳቁስ እና የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግም አሰልጣኙ ጀስ ማርክት ቃል ገብተዋል፡፡

«በዊልቼር ቅርጫት ኳስ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የስፖርት ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማግኘት ተከታታይነት ያለው ስልጠና እና ስፖርቱን የማስተዋወቅ ስራ ሊሰራ ይገባል» የሚሉት አሰልጣኙ፣ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን በቀጣይ በትኩረት ከሰራ ውጤታማ ቅርጫት ኳስ ተጨዋች ማፍራት እንደሚችልም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ዓለሙ ዮሴፍ ከኦሮሚያ ክልል አሰላ ከተማ የመጣ የቅርጫት ኳስ ተጨዋች እና አሰልጣኝ ነው፡፡ የአስልጣኝነት ስልጠናውን እየወሰደ ያለው ዓለሙ ከአሁን በፊት እንደዚህ ዓይነት ስልጠና ላይ እንዳልተሳተፈ ይገልጻል፡፡ በዊልቼር ቅርጫት ኳስ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የስፖርት ዘርፍ ተከታታይነት ያላቸው ስልጠናዎች ከተሰጡ ስፖርቶችን ማሳደግ ቀላል መሆኑን ዓለሙ ይገልጻል፡፡

ለበርካታ ዓመታት በቅርጫት ኳስ ተጨዋችነት እንዳሳለፈ የሚገልጸው ዓለሙ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ስፖርትን ሙሉ በሙሉ እንደማያውቀው የተረዳው በስልጠናው ላይ መሳተፍ ከጀመረ በኋላ መሆኑንም ተናግሯል፡፡ ተጨዋቾች በጨዋታ ላይ የሚሰሯቸው ያልተገቡ አጨዋወቶችን ጨምሮ በርካታ ስህተቶች በስፖርቱ ላይ ያላቸውን አሉታዊ እና አዎንታዊ ተጽዕኖ ስልጠናው እንዳስገነዘበው ዓለሙ ጠቁሟል፡፡

ስልጠናው ቀጥሎ በቀጣይ በተግባር ሲደገፍ ከዚህ በተሻለ ከፍተኛ እውቀት እንደሚቀስም የተማመነው ዓለሙ፣ እንደዚህ ዓይነት ቀጣይነት ያላቸው ስልጠናዎች ከተጠናከሩ በቀጣይ በፓራሊምፒክ ውድድር ላይ በመሳተፍ ስፖርቱን ይበልጥ ለማስተዋወቅ አቅም እንደሚፈጥር ይገልጻል፡፡ ኢትዮጵያም ከሶስት ዓመት በኋላ በሚካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ በዊልቼር ቅርጫት ኳስ ለመሳተፍ ከወዲሁ ጠንክራ መስራት እንዳለባት ዓለሙ ዮሴፍ መክሯል፡፡

የተሰጣቸው ስልጠና የአካል ጉዳተኞችን ደረጃ ለመለየት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሰጣት የምትገልጸው ደግሞ «አዲስ ጉዞ የዊልቼር አቅራቢ እና ጥገና ድርጅት» ን ወክላ የተሳተፈችው ምስሌ ሙሉጌታ ናት፡፡ ድርጅታቸው ከተለያዩ በጎ አድራጊ ድርጅቶች በሚደረግላት ድጋፍ በነጻ ለአካል ጉዳተኞች ዊልቼር እና መለዋወጫዎችን እያቀረበ መሆኑን የገለጸችው ምስሌ፣ ቀደም ሲል የአካል ጉዳተኞችን የጉዳት ዓይነት ሳይለዩ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበረውን አሰራር የሚለውጥ ስልጠና ማግኘቷን ትገልጻለች፡፡

በቀጣይ ለአካል ጉዳተኞች በሚያደርጉት የዊልቼር ድጋፍ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ስልጠናውን ሰፊ እውቀት እንዳስጨበጣት ገልጻ፣ በንድፈ ሀሳብ የተጀመረው ስልጠናው ወደ ተግባር ሲገባ የተለየ ግንዛቤ እንደምትጨብጥ ያላትን ተስፋ ገልጻለች፡፡

«የኢትዮጵያ ዊልቼር ቅርጫት ኳስ ስፖርት በጅምር ላይ ያለ ስፖርት ነው፡፡ ስፖርቱን ይበልጥ ለማስተዋወቅ እና ተዘውታሪ ለማድረግ የራሱ የሆነ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ማቋቋም ያስፈልጋል» ትላለች ሰልጣኟ ምስሌ ሙሉጌታ፡፡

ኢትዮጵያ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽንን አቋቁማ ርብርብ ከተደረገ በፓራሊምፒክ ውድድር ላይ በዊልቼር ቅርጫት ኳስ የሚሳተፉ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሚቻል ምስሌ ገልጻለች፡፡ ስፖርቱ በደምብ አለመተዋወቁ እና የስፖርቱ ቁሳቁስ በቀላሉ አለመገኘታቸው ለዊልቼር ቅርጫት ኳስ አለማደግ ዋና ዋና እንቅፋቶች መሆናቸውን ምስሌ ሙሉጌታ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተናግራለች፡፡

ዊልቼሮች በብዛት እና በጥራት ካለመኖሩ ባሻገር የዊልቼር መለዋወጫዎች በጥራት እና በብዛት አለመኖራቸውም ከባዱ ፈተና እንደሆነ ገልጻ፣ማህበረሰቡ ለአካል ጉዳተኞች የነበረው የተሳሳተ አመለካከት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ማሳየቱ በበጎ ጎን ሊነሳ እንደሚችል እና ይህ በጎ ገጽታ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አዲስ ጉዞ የዊልቼር አቅራቢ እና ጥገና ድርጅትን ወክላ በስልጠናው ላይ የተሳተፈችው ምስሌ ሙሉጌታ ትናገራለች፡፡

በስልጠናው ላይ እየተሳተፉ ያሉ ሰልጣኞችን ሙሉ ወጪ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ኮሚቴ መሸፈኑን ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ከዚህ ስልጠና ባሻገር በቀጣይ የክለቦች እና የከተሞች ውድድር ለማካሄድ እቅድ መያዙ ታውቋል፡፡ ፌዴሬሽኑ ከነዚህ ውድድሮች እና ስልጠናዎች ብቁ ባለሙያዎችን በመለየት ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ዝግጅት እንደሚያደርግም ገልጿል፡፡

 

ታምራት አበራ

 

 

Published in ስፖርት

 

የትናንቱንም አስብ፤ አንገት የተፈጠረው ዞሮ ለማየት ነው። ዓለም ዋዣቂ ናት፤ ከፍና ዝቅ ስትል አትደናገጥ፤ ፀሐይ ዝናብን ተከትላ ትፈነጥቃለች። ያኔ ከመከፋትም በኋላ ትልቅ መፅናናት ይሆናል። ከሌሊት በኋላም ሌሊት አይመጣም። ከኀዘን በኋላ ደስታ ይሆናልና በርታ! መነቀፍን አትፍራ፤ ነቀፋህን ግን አጥራው፤ ስለ ሀሰት ሳይሆን ስለ እውነት ተገፋ፤ ሌሎችን ውደድ ፍቅር ስጦታ እንጂ ብድር አይደለም፤ አልወደዱኝም ብለህ በአበዳሪዎች አንቀጽ አትካሰስ፤ የገባህን አድርግ የዚህ ዓለም ሰው ሲወድህም ሲጠላህም ባለማወቅነው። ብዙዎች ስለወደዱህ ይወድሃል፤ ብዙዎች ስለጠሉህ ይጠላሃል፤ ሁልጊዜ የበላዮችህን አትመልከት፤ የበታቾችህንም ለማየት ሞክር እንጂ።

ለድምፅ አልባዎች ጩህላቸው፣ ለተጠቁት ተሟገትላቸው። እውነት እውነት በማለትህ የምታጣው ሀሰተኛ ወዳጅህን ብቻ ነው። እውነት እውነት በማለትህ የምታተርፈው ግን እውነተኛ ወዳጅን ነው። ደጋፊዎች ተከታዮች አይደሉም። ሰዎች ስለደገፉህም የያዝኩት እውነት ነው ብለህ መንቻካ አትሁን፤ ምናልባት ዛሬ የሚጮሁልህ ዛሬን ሊረሱብህ ሊሆን ይችላል። ሲያለቅሱልህም ቃልህ ማርኳቸው ሳይሆን የሞተ ዘመዳቸው ትዝ ብሏቸው ሊሆን ይችላልና አለቀሱ ብለህ ንግግርህን ድንበር አታሳጣው።

እውነትንም በደጋፊ ብዛት እንዳትመዝናት ተጠንቀቅ። ለእውነታ እንጂ ለይሉኝታ አትኑር፤ ያን ስልህ የምትኖርበት ሕዝብና ባሕል ከእውነት ጋር እስካልተጋጨ መጋፋት የለብህም። ሰዎች የሚቀበሉህ ባሕላቸውን ስታውቅና ስታከብርላቸው ነው።

ልጅነት የለሰለሰ መሬት፣ ወጣትነት የአዝመራ ዘመን፣ ሽምግልና ደግሞ የአጨዳ ዘመን መሆኑን አስተውል። በሽምግልናህ የምታጭደው የወጣትነትህን አዝመራ ነውና ዛሬ ለምትዘራው ተጠንቀቅ። የሰዎችን ያለማወቅ አግዝ፤ ዕውቀትህ ባላወቁት ላይ እንድትኮራና እንድትፈርድ አያድርግህ፤ የአዋቂ ኩሩ ቁጥሩ ካላዋቂዎች ነውና ማወቅ ባለዕዳነት እንዳይሆን አላዋቂዎችን እርዳቸው። ዛሬ የመዝራት ዘመንህ ነገ መከራህ ነውና በእምነት እውነትን ዝራ፤ በምታውቀው ቦታ ላይ አገልጋይ በማታውቀው መልካም ተግባር ላይ ደጀን ሁን፡፡

በቦታህ መምህር ያለቦታህ ተማሪ ሁን፤ ክብሩ እንዳይቀንስብህ ከዕቃ ትምክህት፣ ከዕውቀት ሙግት ራቅ። ሁሉን ወሬ ላውራ አትበል፤ የደበቁህን ምስጢር አታውጣጣ፤ የሰማኽውን ወሬና የተገለጠልህን ምስጢር ምን መፍትሔ ሰጠኸውና? ያየህውን ሥራ ሁሉ እሰራለሁ፣ የሰማኸውን ትምህርት ሁሉ እማራለሁ አትበል። ይህ የተሰወረው የቅንዓት ጠባይ ነውና ሁሉን ልያዝ ማለትም ዝንጉ አድርጎ እንዳያስቀርህ ሁሉም ውስጥ ልኑር አትበል።

ቆንጆዎች ቁንጅናቸው ሁሉን የሚተካ እየመሰላቸው ከዕውቀትና ከትሕትና ይርቃሉ። ሁሉንም ሰው በመልካቸው የሚማርኩት ስለሚመስላቸው ኩሩና ተንኮለኞች ይሆናሉ። አንተ ግን ቆንጆ ወዳጅን እንጂ ቆንጆ ቁመናን አትሻ፤ ቆንጆ ትዳርን እንጂ ቆንጆ ሴትን አትመኝ፤ የላይ ነገር ከንቱና ኃላፊ ነውና በሚፈርስ አካል፣ ኑሮ በሚለውጠው መልክ አትደለል። እወድሃለሁ ብለህ የምትናገረውን ቃል ውለታ አታድርገው፤ መውደድህን የምትናገረው እንወድሃለን እንዲሉህ አይሁን፤ ሠላም ያለው አፍቃሪ የራሱን ፍቅር ያለ ምክንያት መፈፀም የሚችል ብቻ እንደሆነ እወቅ። መወደድህን ለመስማት አትጠብቅ፡፡

የሰዎችን ያለማወቅ አግዝ፤ ዕውቀትህ ባላወቁት ላይ እንድትኮራና እንድትፈርድ አያድርግህ፤ የአዋቂ ኩሩ ቁጥሩ ካላዋቂዎች ነውና ማወቅ ባለዕዳነት እንዳይሆን አላዋቂዎችን እርዳቸው። ዛሬ የመዝራት ዘመንህ ነገ መከርህ ነውና።

ምንጭ፡- ድረ ገጽ

 

መርድ ክፍሉ

 

 

 

Published in መዝናኛ

 

ለውጥ የሚለውን ቃል መመሰቃቀል ከሚለው ቃል ጋር ማቆራኘት ቢቻልም፤ ለውጥ ማለት መመሰቃቀል አይደለም፡፡ ነገር ግን ለሚገኘው አዲስ ነገር ዋጋ መክፈል ነው፡፡ ለውጥ የሚለውን ቃል ስናስብ በብዙ ልፋት እና ትግል ውስጥ አስደሳች፣ አዲስ፣ ብሩህ ተስፋን የያዘ ሃሳብ ነው፡፡

በሕይወትህ ውስጥ ለውጥ መጣ ማለት ሽንፈት መጣ ማለት አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለውጦች ስቃይን፣ አሳዛኝ ሁኔታን፣ ብዙ ትግሎችን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ለውጥ ውጤቱ ድል፣ ደስታ እና ስኬት የሚከተሉት ጣፋጭ ጉዞ ነው፡፡ ለውጥ ዋጋ ከማስከፈል አንጻር ሰዎችን ከሰውነት ተራ የማስወጣት ጉልበት አለው፡፡ ነገር ግን ለውጥ እኛን የተሻልንና ምሉዕ የማድረግ ኃይል አለው፡፡ አንድ ሰው ወይም አንድ አገር አመለካከቶቹን በለወጠ ወይም ደግሞ ባጎለበተ ቁጥር ሰውዬው እንዳልሞተ ወይም ደግሞ ብሩህ ተስፋ እንዳለው ማየት ይቻላል፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ ለውጦች በሕይወታችን ውስጥ ሲከሰቱ አንዳንድ ጠቃሚ የሕይወት ዕሴቶቻችንን ጠብቀን ማቆየት እንዳለብን ማስታወስ አለብን፡፡ አንድ ታዋቂ ደራሲ እንዳለው ለውጥ ያለፈውን ደምስሶ መቅዳት ማለት አይደለም፡፡ እናም ማቆየት ያለብንን የጥንቱን ማቆየት እንዳለብን እናስታውስ፡፡ ለምሳሌ፦ ትልልቅ ሰዎችን ማክበር ጥሩም አስፈላጊም ነው፣ ታሪካዊ ቦታዎቻችንን መጎብኘትና አባቶቻችን ያቆዩልንን ቅርጻቅርጾች መመልከትም፣ መጠበቅም ወሳኝ ነው፡፡

በቤታችን ውስጥ የምንጠቀምባቸው የቤት ዕቃዎች ብዙዎቹ ቀድሞ የምንጠቀምባቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን ቆየት ያሉ ዕቃዎችን ጠብቀው ያስቀመጡ ብዙ ሰዎች አሁንም አሉ፡፡ የእኛ የሕይወት ስብዕናም እንደዚሁ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሕይወት ተመሳሳይ አይደለችም። ሁኔታዎቻችን በእርግጥም ይለወጣሉ፡፡ ነገር ግን አሁንም ከእኛ የቀሩ አንዳንድ ሰብአዊና መንፈሳዊ እሴቶች አሉ፡፡

በለውጥ መካከል እያለንም እንኳን በሕይወታችን በጣም አስፈላጊ ናቸው ብለን የምናስባቸውን ነገሮች መለየትና ምንም ይሁን ምን እነሱን ለመጠበቅ መትጋት በሕይወታችን ውስጥ ከሚያስደስቱንና ከሚያበረታቱን ነገሮች አንዱ ነው፡፡ እነዚህን ለውጥ አልባ እሴቶቻችንን መጠበቃችን ጥንካሬ እጅጉን ባስፈለገን ጊዜ ብርታትን ይሰጡናል፡፡ በእርግጥም እራሱን መጣል የሚፈልግ ሰው የለም። ሁላችንም እራሳችንን ለመጠበቅ የተቻለንን እናደርጋለን። ንጹህ ለመልበስ፣ ውበታችንን ለማቆየት፣ የምንበላውን ማዘጋጀት፣ የለንም ከምንለው ጊዜ እንደምንም ብለን ለመሻማት እንሞክራለን። ለውጫዊ ማንነታችን የተቻለንን ጊዜ፤ የተቻለንን ገንዘብ መስዋት እናደርጋለን።

ችግሩ ግን የሕይወታችን መሠረቱ የውጫዊ ማንነታችን ነው። ትልቁን አትኩሮት እና እንክብካቤ የሚሻው ውጫዊው አካላችን ሳይሆን ውስጣዊው ማንነታችን ነው። አሁን ላለንበት ሁኔታም ሆነ ለመረጥነው የሕይወት ጎዳና ትልቁን ድርሻ የሚይዘው አዕምሯችን ነው። ይህ በቅድሚያ ከምንም ነገር በላይ ማመን ያለብን እውነታ ነው (ይህንን ማመን የተሳነው ሰው፤ ቀሪው ነገር ትርጉም አይሰጠውም)። ይህንን እውነታ በቅጡ መረዳት ከቻልን፤ ኑሮአችንን ለሚመራው አዕምሯችን የምንሰጠውን አነስተኛ ጊዜ እንታዘባለን።

አንድ መኪና ያለሹፌር ሞተሩ ተነስቶ ቢለቀቅ፤ በእርግጠኝነት ቀጥ ብሎ ለመጓዝ አይቻለውም። የመኪና መሪ እንደዘበት ያለ አትኩሮት የሚተው አይደለም። መኪናው ከታሰበበት ቦታ ለመድረስም ሆነ ከአደጋ ለመጠበቅ መሪው በደህና ሹፌር እጅ መጨበጥ አለበት። ሊረጋገጥ የሚገባው ነገር የተሳፋሪው ምንነት ሳይሆን የሹፌሩ ነው። ስለዚህም አዕምሯችንን በአግባቡ እና በተለያዩ እውቀቶች መመገብ ተገቢም አስፈላጊም ተግባር ነው፡፡

 

መርድ ክፍሉ

 

 

Published in መዝናኛ

የመስቀል በዓል በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት ይከበራል። ምንም እንኳን ኃይማኖታዊ በዓል ቢሆንም ይዘቱን ሳይለቅ የተለያዩ ባህላዊ እሴቶች ታክለውበት ደማቅ ክብረ በዓል ሆኗል። ለእዚህም ይመስላል በርካታ ሰዎች ይህንን በዓል በዚያ አካባቢ ለማክበር የሚተሙት። በተለይ በጉራጌ ብሄረሰብ ዘንድ የሚካሄደውን የበአል አከባበር ለመታደም ብዙዎች ወቅቱን ጠብቀው ወደ ስፍራው ያመራሉ። ለዛሬ በጉራጌ ብሄረሰብ በተለይ ሶዶ ክስታኔ እና በሰባት ቤት ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ለቀናት የተሰጠውን ስያሜና የተለያዩ ተግባራት እንቃኛለን።

ቀናት እንደ የባህሉ የተለያየ ስያሜ ይሰጣቸዋል፡፡ የተለያየ ተግባራትም ይከናወንባቸዋል፡፡ በጉራጌ ብሄረሰብም የመስቀል በዓል ሰሞን ያሉት ቀናት የየራሳቸው ስያሜ ተችሯቸዋል። የተለየ ክንውንም ያስተናግዳሉ፡፡ በጉራጌ መስቀል ከመድረሱ ከሶስት ወር በፊት የተለያዩ ዝግጅቶች የሚከናወኑ ቢሆንም፤ በተለይ ከ12 ቀደም ብሎ ያሉት ቀናት ልዩ ቦታ አላቸው፡፡

በጉራጌ ባህል እንደየአካባቢው ቢለያይም የመስቀል በዓል መከበር የሚጀምረው ከሦስት ወራት ቀድሞ ነው። ለአብነት በሰባት ቤት ጉራጌ ከሦስት ወራት በፊት ቀድሞ ዝግጅት ይደረጋል። ወቅቶችም የተለያየ ስያሜም አላቸው። ለበዓሉ ሁለት ወር ሲቀረውም ጉረንቻድ (የእንሰት ግንድ) በማለት የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ። የበዓሉን መድረስ በመጠባበቅ የእንሰት ንጉሶች በሚባሉት ጓሪ፣ አስታራ፣ ቅምናርና የተለያዩ ምግቦች ይዘጋጃሉ።

አዲስ አመት «» ሲባል ማለትም መሰከረም ሁለት ቆጮ በሚገባ ያዘጋጁና እለቱን በድምቀት ያከብሩታል። በመቀጠል በ12 ደመራ ይቆማል፡፡ ይህ ሲደረግ ለአዛውንቱና ለልጆች ተብሎ በተናጠል በማዘጋጀት ነው። በዚህ እለትም ደመራው የሚቆመው የልጆች ሲሆን፤ በ13 ላይ ይለኩሱታል። በጉራጌ ባህል መስከረም ወር የሰርግ ወቅት በመሆኑ ልጆችን ለመዳር ቤተሰቡ ብዙ ይለፋል፤ ጎረቤቱም ቢሆን የተቻለውን ለማድረግ ወይም ለማገዝና ለበዓሉ የሚሆኑ ዝግጅቶች ልዩ እንዲሆኑ ደፋ ቀና ይላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እንቅልፍ አጣ የሚሉት ቀን ይደርሳል፤ ማለትም መስከረም 13 ይህ ቀን ስያሜውን ያገኘበት ዋና ምክንያት ለድሆች የሚያበረክቱትን ሲያዘጋጁ፣ ለሰርጉ፣ ለጎረቤቱና ለበዓሉ ፣ ለማን ሰጥቼ ለማን ልተው የሚለውም ጉዳይ ስለሚያስጨንቃቸው ወንዱም ሆነ ሴቱ እንቅልፍ ሳያይ ስለሚያድር ነው። አሁን ደግሞ ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው መስከረም 14 ሲሆን፤ የሆምያ ወይም ደግሞ ፊት በማለት ይጠሩታል። ይህም ቀን እንደላይኛው የተለየ ትርጓሜ ያለው ሲሆን፤ መስቀል ጀመረ ለማለት እንደሚጠቀሙበት የአካባቢው አዛውንቶች ያስረዳሉ።

15 ደግሞ የእርድ ቀን ሲሆን፤ ጨርቆስ በማለትም ይጠራል። ያው እንደሚታወቀው በኃይማኖቱ ቀኑ ህጻኑ ቂርቆስ የሚውልበት ሲሆን፤ ይህንን በዓልም በዚህ የሰየሙበት ምክንያት ህጻኑ ቂርቆስ ህጻን ስለሆነ የለመነውን እግዚአብሔር ይሰማዋል የሚል እምነት ስላለ የተጣላው ታርቆ በአንድነት ማንም ቂም ሳይዝ እርዱ ላይ የሚሳተፉበት እለት እንዲሆን ታስቦ ነው። ስለሆነም በዚህ ቀን የሚለመን ነገር ሁሉ ውጤታማ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል። እናም በዚህ ቀን ሰላም እንጂ ጸብ አይፈቀድም፤ አልታረቅም ማለትም አይቻልም፤ ከተረገመም ይደርሳል ተብሎ ስለሚታመን እርግማንም እንዳይኖር የተለየ ጥረት ይደረጋል። ስለዚህም ይህ ቀን ለጉራጌዎች የተለየ ትርጉም አለው።

በሰባት ቤት ጉራጌ በ16ኛው ቀን በሁሉም ቦታ እንደሚደረገው ደመራ ይለኮሳል፡፡ አባቶች ለአገር ሰላም፣ ለህዝቡ ጤንነት፣ ለምድሪቱ በረከት ይለምናሉ፤ ምርቃታቸውንም ይቸራሉ። በ17 ደግሞ ንዑባር ወይም ደግሞ ታላቅ ቀን በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ ሁሉም ያገባ ሰው ቤተሰቡን ወይም እናት አባቱን ለመጠየቅ የበሬ ሻኛ እየያዘ የሚሄድበት እለት ነው። በ18 ደግሞ ትንሽ ባር ይባላል። ይህ የተባለበት ምክንያትም ከእናትና አባት ውጭ ያሉ ቤተሰቦች የሚጠያየቁበት ስለሆነ ከዚያ ያነሰ የመጠያየቂያ ቀን በመሆኑ ነው።

እንዲህ እየተባለ እስከ መስከረም 24 ድረስ ይቆያል። ይህ ቀን ማጆያ ወይም ደግሞ ተጠናቀቀ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፤ በወቅቱም ከሁሉም ቦታ የተሰበሰበው የጎድን ሥጋ የሚበላበት እለት ነው። ያው እስከዚህ እንዴት ቆየ ማለታችሁ አይቀርምና የጉራጌ ሴቶች ለየት የሚያደርጋቸው ይኸም ነው። እንዳይበላሽ አድርገው በባህላዊ መንገድ ያቆዩታል። በእለቱም ይቀቅሉትና ምንም የተለየ ጣዕም አለማምጣቱን ካረጋገጡ በኋላ በሚገባ አዘጋጅተው ያቀርባሉ። ከዚያም «መስቀል ያረንረ ድርጉም ዘኩንረ ያሆሆዬ» በሚል ጨዋታ ስንብት ይደረጋል። ትርጓሜውም መስቀል እየሄደ ነው መጥታችሁ መልሱልን ማለት ነው። ስለዚህም መስቀል ሁል ጊዜ ከእነርሱ ጋር እንዲሆን የሚመኙበት እለት መሆኑን ያበስሩበታል። ለሚቀጥለው አመት በሰላም በጤና ያገናኘን በማለትም አባቶች ከመረቁ በኋላ በዓሉ ይጠናቀቃል።

በሶዶ ክስታኔ ደግሞ እንደ ሰባት ቤቱ ሁሉ የራሱ የአከባበር ባህሪ አለው። በእርግጥ በትንሹም ቢሆን የሚጋሩት ነገር እንዳለ ልብ ሊባል ይገባል። ምክንያቱም በዓሉ የጉራጌ ነዋ። በሶዶ ክስታኔ የመስቀል በዓል መስከረም በገባ በ13ኛው ቀን ነው የሚጀምረው። ከአገር ውጪም ሆነ በአገር ውስጥ ያለው የብሔሩ ተወላጆች እንዲሁም ሌሎች ታዳሚዎች እለቱ ሳይደርስ ለበዓሉ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በመግዛት ይዘጋጃሉ። የብሔሩ ተወላጆች የመስቀል በዓልን ለማክበር ከያሉበት ወደ ትውልድ አገራቸው የሚያቀኑትም ቀደም ብለው ነው።

ለመስቀል በዓል አገሩ ያልገባ የብሔሩ ተወላጅ ካለ «ሞቷል» ተብሎ ስለሚታመን እንደምንም ብሎ በዓሉን ከወዳጅ ዘመድ ጋር ማሳለፍ ግድ ነው። ለበዓሉ አገር ቤት የገባም የተለያዩ ባህላዊ ሥርዓቶችን በመፈጸም እስከ መስከረም 21ቀን ድረስ ይቆያል። በሶዶ ጉራጌዎችም ከመስከረም አስራ ሁለት እስከ አስራ ስምንት ድረስ ያሉት ቀናት የተለያየ ስያሜ አላቸው። ይሁን እንጂ በዓሉ ግን እስከ ጥቅምት አምስት ድረስ ይቆያል።

መስከረም13 «ወልቀን» ተብሎ ሲጠራ ትርጓሜውም የሴቶች ቀን በመባል ይታወቃል። በዚህ ጊዜ ሴቶች ጎመንና ዓይብ በማዘጋጀት አጠቃላይ ቤተሰቡ ተሰባስቦ እንዲመገብ ያደርጋሉ። ይህን የሚመገቡት የቤተሰቡ አባላት በየራሳቸው በተዘጋጀላቸው «ጣባ» አማካኝነት ነው። ጣባዎቹ ተሰቅለው ከተቀመጡበት ለመስቀል በዓል ብቻ የሚወርዱ ሲሆን፤ በቤተሰቡ ልክና በየስማቸው የተዘጋጁ ናቸው። ተለይቶ የማይሰጠው ባልና ሚስት ለሆኑ ብቻ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ባልና ሚስት አንድ አካል አንድ አምሳል ናቸው ተብሎ ስለሚታሰብ ነው። ምግቡ የሚበላው ጅባ ተነጥፎ በላዩ ላይ አንጮት የሚባል የምንጣፍ አይነት ተደርቦበት ቤተሰቡ ተደርድሮ እንዲቀመጥ ከተደረገ በኋላ ነው።

መስከረም14 ደግሞ «ደንጌሳት» በመባል ሲጠራ ዕለቱ የልጆች ወይም የሕፃናት ቀን ይባላል። ይኸውም ልጆች በትንሹ በሰፈር አካባቢ ደመራ ደምረው የሚጫወቱበት ቀን ነው። በዚህ ቀን ቆጮ ይጋገራል፤ ጎመን ይቀቀልና ተከትፎ በቅቤ ታሽቶ ይዘጋጃል። ከዚያም ከአይብ ጋር ይቀላቀላልና ህጻናቱ ደመራ አብርተው እስኪጨርሱ ድረስ ይጠበቃሉ። ይህ ደመራ በጉራጌኛ ምጅር ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፤ ደመራውን አብርተው ካጠናቀቁ በኋላ አባቶችና እናቶች ይመርቋቸዋል። ከዚያ ወደተዘጋጀላቸው ደዋወሸት ወይም ጎመንና አይብ ተቀላቅሎ ወደተዘጋጀው ምግብ ይሄዳሉ። በተዘጋጀላቸው ጣባም ምግቡን ተቀብለው በአንቀፎ ወይም የቀንድ ማንኪያ ይመገባሉ።

መስከረም15 ሲደርስ ደግሞ «ጨርቆስ» ብለው በሚጠሩት ልዩ በዓል ተጠምደው ይውላሉ። ይህ እለት የዕርድ ቀን በመባልም ይነገራል፤ 16 እና 17 የሚያርዱ እንዳሉ ሆነው። ዕለቱ ዕርድ የሚፈጸምበት በመሆኑ የሚታረደው በሬ ሽማግሌዎች ፊት ቀርቦ ሽማግሌዎች ስለአገር ሰላምና በዓሉን በተመለከተ እያነሱ ይመርቃሉ፤ መልካም ምኞታቸውንም ይገልጻሉ፤ የቤተሰቡ አባላትም ሦስት ጊዜ «ኬር ይሁን» በማለት ምርቃቱን ያጎርፉታል። ትርጉሙም «ሰላም ይሁን» ማለት ነው። በእዚህ ባህላዊ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንዲመርቁ የሚጋበዙት ሴቶች ወይም ወንዶች ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁንና ለማሳረጊያነት የሚሆነውን ምርቃት ሁሌም የሚመርቀው ወንድ እንጂ ሴት አይሆንም። ዕለቱ አንዳንድ ጊዜም የጥሬ ሥጋ ቀን በመባል ይጠራል። ምክንያቱ ደግሞ በዕለቱ የሚበላው ጥሬ ሥጋ በመሆኑ ነው። ዕርዱ በግል ወይም በጋራ ሊከናወን ይችላል። በዕርድ ክፍፍል ወቅት የታረደውን በመከፋፈል ለሚስኪኖች እንዲደርስ ይደረጋል። በዚህ ደግሞ ማንም ተቃውሞ አያደርግም።

መስከረም 16ን ደግሞ ሶዶ ጉራጌዎች «የብርንዶ ወይም የክትፎ ቀን» ይሉታል። የጉራጌን ባህላዊ የአመጋገብ ሥርዓትን ከሚያመላክቱ መሠረታዊ ነገሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው ይህ ቀን። ዕለቱ ለየት ያለና ትኩረት የሚሰጠው ሲሆን፤ በዚህ ቀን ትልቁ ደመራ የሚደመርበት፤ ጎረምሳና ልጃገረዶች በባህላዊ ጭፈራ የሚተያዩበት ቀን እንደሆነ ይነገራል።

መስከረም17 ላይ ሲደረስ ደግሞ «ከሰል» የሚባለውን ቀን የምናገኝበት ነው። ይህ ጊዜ ሁሉም የቤተሰብ አባላት ደመራው ወደተደመረበት ቦታ በመሄድ ከሰሉን እየረገጡ የሚሻገሩበትና ዘመኑ መልካም እንዲሆንላቸው የሚማጸኑበት እለት ነው። ከሰል መጥፎው ወይም ጥሩ ያልነበረው ነገር የጠፋበትና ብርሃን የታየበት ዕለት ማብሰሪያ ተደርጎ ይታሰባል። ከዚያም ባሻገር የአዲስ ዓመት መግቢያና የዘመን መለወጫ ዕለትም በመሆኑ ሁሉም የራሱን ዕቅድ ይዞ ለመልካም ነገር የሚነሳበትም ነው ይላሉ የአገሬው ሰዎች።

ከመስከረም 18 እስከ መስከረም መጨረሻ ያሉት ቀናት ደግሞ «አዳምና» ወይም «የገበያ ላይ ጨዋታ» በመባል የሚታወቀው ሲሆን፤ በእነዚህ ቀናት ልጃገረዶችም ሆኑ ጐረምሶች በነፃነት ማንም ሳይገድባቸው የሚጫወቱበት እለት ነው። ጨዋታውም የሚፈጸመው ገበያ ባለበት ሁሉ እየተዘዋወሩ ሲሆን፤ በተለይ ከሌሎች ቦታዎች የመጡ ወንዶች ለወደፊት ሚስት የምትሆናቸውን ሴት የሚመርጡበትና ሴቷም ብትሆን የምትታጭበት ጊዜ መሆኑ በጉራጌዎች ዘንድ ይታወቃል። በእነዚህ ቀናትም ልጃገረዶቹም ሆኑ ወንዶቹ አሸብርቀው ደምቀው ነው የሚታዩት። ምክንያቱም ምርጫቸው እንዲበላሽ አይፈልጉማ ። እናም ይህ ወቅት ትዳር የመመስረቻ፣ አዲስ ለማግባት የሚታጭበት፣ ደስታን ከቤተሰብ ጋር ማሳለፊያና የአዲስ ዓመት ውሎውን ማሳመሪያ ነው። ለእርሱ አዲስ ዘመን ማለት ነው። እናም ዓመቱን ሙሉ የለፋበትን ለዚህ ቀን በማዋል ምርቃትን በመሰነቅ ቀጣዩን የተስፋ ቀኑን የሚቀበሉት ልዩ ጊዜው ነው።

 

ጽጌረዳ ጫንያለው

Published in ማህበራዊ
Sunday, 01 October 2017 19:21

የኢሬቻ በዓል

ባህል የአንድ ህዝብ ማንነት አንዱ መገለጫ ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብም እንደማንኛውም ህዝብ ማንነቱን የሚገልፁና የሚያስተዋውቁ ብዙ ባህሎች እንዳለው ይታወቃል፡፡ ከዚህ ውስጥ ኢሬቻ በዓል አንዱ ሲሆን የጋብቻ፤የአምልኮና የአለባበስ ባህሎችን በጥቂቱ መግለጽ ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ ኦሮሞ በህይወት ዘመኑ ውስጥ በሚያከናውናቸው ነገሮች በሙሉ የሚመራበት ስርዓት አለው ማለት ነው፡፡

በኦሮሞ ገዳ ስርዓት ውስጥ የኢሬቻ በዓል ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና በስፋት የሚታወቅ በዓል ነው፡፡ ይህም የህዝቡን ማንነት፤ ሰላምና አንድነትን የሚያንጸባርቅ ስለሆነ ከ8 ተኛው ምዕተ ዓመት በፊት ጀምሮ እየተከበረ ዛሬ ደርሷል፡፡ ይህ በዓል የክረምት ወራት አልፎ መስከረም ሲገባ ከመስቀል በዓል በኋላ ይከበራል፡፡በዓሉም የኦሮሞን እምነት፤ ወግና የአኗኗር ሁኔታን ቀጥታ እንደሚያንጸባርቅ የገዳ ስርዓት አባቶች በተለያዩ ጊዜያት ይገልጻሉ፤ በዚህ ዘርፍ በተደጋጋሚ ጥናት ያካሄዱ ምሁራኖችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡

ኦሮሞ ለፈጣሪውም ትልቅ ቦታ ስለሚሰጥ እሱን የሚያመልክበትና የሚያመሰግንበት ልዩ ቦታዎችን በመሄድ አምላኩን ያመሰግናል፡፡ ከዚህ ውስጥ ኢሬቻ አንዱ ሲሆን፤ ሰማይና ምድርን ለፈጠረው አምላክ ትልቅ ቦታ ሠጥቶ የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ በኦሮሞ ዘንድም ለፈጣሪ ፍርሃትና ከበሬታ መስጠት የመነጨውም ከዚህ መሆኑን ያሳያል ማለት ነው፡

የኦሮሞ ህዝብ አንድ ፈጣሪ መኖሩንም ያምናል፡፡ ለዚህም ወደ ተራሮች፤ ከፍታዎችና ወንዞች አጠገብ በመሄድ ለፈጣሪው መስዋዕት ያቀረባል እንጂ አያመልካቸውም፡፡ ይሄ ደግሞ ኢሬቻ ነው ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የኢሬቻ በዓል የሚከበረው ህዝቡ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት በዓል ሲሆን ከዚህም ያለፈ ትርጉምም አለው፡፡ በአሮጌው ዓመት ከፈጣሪ ስላገኙት ምህረትና ጸጋ በአዲሱ አመት ልዩ ምስጋና የሚያቀርቡበት ቀን ስለሆነ በታላቅ ስነ-ስርዓት ሲከበር ቆይቷል፤ አሁንም እየተከበረ ይገኛል፡ በተጨማሪም በዓሉ የኦሮሞ ሕዝብ ስለ ሠላም፣ ጤና፤ ሀብትና ስለሀገር አንድነት ለፈጣሪያቸው ምስጋና የሚያቀርቡበት ሥርዓት ከመሆኑም በላይ የእርቅ ምልክት እንደሆነ የተለያዩ መጽሐፎች የገዳ አባቶችን ዋቢ በማድረግ ያብራራሉ፡፡

ኢሬቻ በገዳ ስርዓት ውስጥ ትልቅ ቦታ ሲኖረው የዚሁ አንድ አካል ነው፡፡ የገዳ ስርዓት የኦሮሞ ህልውና ሲሆን ባህሉን፤ ማህበራዊ ኑሮውን፤ ኢኮኖሚውን፤ አስተዳደራዊ ስርአቱን፤ እንዲሁም ፖለቲካውና እምነቱን የሚያንፀባርቅበት በዓል በመሆኑ ነው፡፡

ስለዚህ ኦሮሞ በኢሬቻ ስርዓት በማካሄድ ፈጣሪ ሁሉን ማድረግ መቻሉንና ሀይል የእሱ ብቻ መሆኑን ይገልፃል፡፡ ለዚህም፤ ፈጣሪ ሆይ! ቅጠልን እህል የምታደርግ! ደምን ወደ ሰው የምትቀይር ምስጋና ለአንተ ይሁን! በማለት ገና ሲነሳ ያመሰግናል፤ በኢሬቻ በዓል ስነስርዓት ሲካሄድም ይህንኑ ይላል፡፡

ገበሬ በፈጣሪ ላይ ተስፋውን በመጣል ዘርን በማሳው ላይ ይዘራል፡፡ ዝናብ ሲዘንብም እህል ይበቅላል፡፡ ይህ ደግሞ የተዘራው እህል ፍሬ አፍርቶ ከግዜ በኋላ ለሰው ልጆችና እንስሳት ምግብ ይሆናል፡፡ ይህ የሚሆንበት ጊዜ ደግሞ በክረምት ወራት ሲሆን ዝናብ በሀይል ከመዝነቡ የተነሳ ወንዞች ይሞላሉ፤ አካባቢዎችም እንዲጨላልሙ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ ወቅቶች ስለሚለዋወጡ መስከረም ሲጠባ ጨለማ የነበረ ወደ ብርሃን ይለወጣል፤ ይጨቀይ የነበረው መንገድ ይደርቃል፤ የተዘራው እህል አብቦ ፍሬውን ያሳያል ፤እንዲሁም እሸት ደርሶ የሚበላበት ጊዜ ይሆናል ማለት ነው፡፡

እንግዲህ የኢሬቻ በዓል የሚከበረው በዚህ ወቅት ሲሆን ኦሮሞ እንኳን ከጨለማ ወደ ብርሃን ወቅት አንኳን አደረሳችሁ ይላል፡፡ምክንያቱም የፀደይ ወቅት(ብራ) አበባዎች የሚያብቡበት ጊዜ ስለሆነ ነው፡፡ ልጆች የደረሱ እሸቶችን በመብላት ይጫወታሉ፤ወይፈንና ጊደር የወቅቱን ፀሐይ በማሞቅ ተደስተው ይቦርቃሉ፤ በደጅም ይፎካከራሉ፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ኦሮሞ የፈጣሪን ሀይል እየተረዳ ይሄዳል፡

የኦሮሞ ህዝብ መስከረም ወር ሲገባ ልዩ ቦታ ስለሚሰጥ ከመስቀል በኋላ በአስቸጋሪ ሁኔታ ያሳለፈውን አምላክ ያመሰግናል፡፡ ይሄ እንግዲህ ኢሬቻ በመባል ይታወቃል፡፡ ኢሬቻ ባህላዊ አምልኮ ሲሆን ኦሮሞ ከጥንት ጀምሮ የፈጣሪ ፀጋ በሀይል ይገለጥበታል ብለው የሚያምኑበት ወደ ሁለት ቦታዎች በመሄድ ስርዓቱን ያካሂዳሉ፡፡ እነሱም ተራራ ላይ የሚደረግ ኢሬቻና ወንዞች አጠገብ የሚካሄድ ነው፡፡ የተለያዩ ቦታዎችንም እንደ ሁኔታው ይመርጣል፡፡ የሆራ አርሰዴ ኢሬቻ ግን ከመስቀል በኋላ የሚከበረው የዛሬው ማለት ነው፡፡

ተራራ ላይ የሚከበረው ኢሬቻ የበጋ ወራት አልፎ የበልግ ዝናብ ይመጣል ተብሎ የሚገመትበት ጊዜ ነው፡፡ምክንቱም በጋ ከፍተኛ ሙቀት ስለሚሆን የመሬት እርጥበት ይጠፋል፤ ሳር ይደርቃል፤ውሃማ ስፍራዎችም በጣም ይቀንሳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሲቆይ በሰውና እንስሳት ሀብት ላይ ጉዳትን ስለሚያስከትል በመጋቢት ወር ውስጥ የኦሮሞ ሽማግሌዎች ተራራ ላይ በመሰባሰብ እጃቸውን ወደ ሰማይ በመዘርጋት እንዲህ ብለው ፈጣሪን ይለምናሉ፡፡ «ዝናብ አታሳጣን፤ወቅቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው ይምጡልን፤ዝናብ ስጠን»በማለት የእግዚአብሄርን ምህረት ይጠይቃሉ፡፡የሚደረገውም ተራራ ላይ ሲሆን ይህ የልመና ስርዓትም የጥንት ኩሾችን ባህልና ፍልስፍና ጋር ቀጥታ ይመሳሰላል ይባላል፡፡

በወንዞች አጠገብ (መልካ) የሚደረገው ኢሬቻ ግን የክረምት ወራት አልፎ መስከረም ሲገባ ነው የሚካሄደው፡፡ይሄም የጉም ወይም የጨለማ ጊዜ አልፎ የብርሃን ወር ስለሚገባ ወቅቱ ለሁሉም ይመቻል፡፡ ዘመድም ከዘመዱ ጋር የሚገናኝበት ስለሆነ ሁሉንም ይስባል፡፡

ከዚህ በመነሳት ኢሬቻ የምስጋና ቀን መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡በዚህ በዓል ላይ የኦሮሞ ህዝብ እንደየእድሜያቸው የባህላቸውን ልብስ በመልበስና የተለያዩ ጌጣጌጦችን በማድረግ፤ እርጥብ ሳርና አበባዎችን በመያዝ በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዴ ወንዝ አጠገብ ሄደው ፈጣሪን ያመሰግናሉ፡፡

የገዳ አባቶች ከለቻ፤ ቦኩ፤ሳር፤ አለንጋና የስልጣን ዱላን ይዘው እንዲሁም ህጉንና ስርዓቱን ጠብቀው በሰልፍ ወደ መልካ(ሆራ አርሰዴ ወንዝ አጠገብ) ይንቀሳቀሳሉ፡፡የሰዎችም አለባበስ ፈጣሪን በሚያስደስት ሁኔታ መሆን ስላለበት አባቶች፤ እናቶችም ሆኑ ወጣቶች በአጠቃላይ ረዣዥም የሆኑ ልብሶችን መልበስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህም ፈጣሪን ያስደስታል ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ የኢሬቻ ስነስርዓት ሲካሄድበት ቆይቷል፡፡

በመላው ሀገሪቷ ውስጥ የሚኖሩና ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሔረሰብ በዚህ በከበረ ቀን ባህላዊ ልብሶችን በመልበስ፤ እርጥብ ሳርና አበባዎችን በመያዝ «ፈጣሪን እናመሰግናለን፤ እንለምናለን፤ ፍጥረታትን የፈጠረ አምላክን እናደንቃለን » በማለት ሆራ አርሰዴ ይሄዳሉ፤ እዛም ያመሰግናሉ፡፡

ኦሮሞና ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችን አካቶ በየዓመቱ ሆራ አርሰዴ የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ይህ ሁሉ ሰው ስርዓቱን በመጠበቅ ወንዙ አጠገብ ሄደው አንገታቸውን በውሃ በመንከር «እድሜ ስጠኝ፤ ስኬትን ስጠኝ፤ ስለምታደርግልኝ ተመስጌን» በማለት ስርዓቱን ያከናውናሉ፡፡በዚህ አምላካቸውን አመስግነው ወደየቤቶቻቸው ሲመለሱ የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችን ከጎረቤቶቻቸው ጋር እንኳን አደረሰን በመባባል ይበላሉ፤ይጠጣሉም፡፡

በሆራ አርሰዴ ላይ የሚከበረውን ኢሬቻ የሚሳተፉት በአካባበው የሚኖሩ የቱለማ አሮሞዎች ብቻ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን የኦሮሞ ህዝብና ሌሎችንም ህዝቦች በህብረት በቦታው እንዲገኙ ማድረግ ችሏል፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ የገዳ አባቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ አዳዲስ ሀሳቦችን በማፍለቅ የህዝቦችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ውስጥ እንዲሳተፉ አድርጓል፤እያደረገም ይገኛል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ወጣቱ ሀይል ተረስቶ የነበረውን ባህል፤እምነትና ወጉን በማስተዋወቅ ለትውልድ እንዲቆይ እያደረገ ይገኛል፡፡

(ይህንን ፅሁፍ ለማዘጋጀት በገዳ ስርዓት ላይ የተጻፉ መጽሐፍቶችን ዋቢ አድረገናል፤በዋናነት ግን የአቶ ጫላ ሶሪ ”ኢሬቻና ገዳ” የሚል በ2008 .ም ካሳተሙት መጽሐፍ ተጠቅመናል)

 

ተካልኝ ማሞ

Published in ማህበራዊ

እርጅና አልፈተናቸውም በየጊዜው በቴአትር ዘርፍ እድሜ ሳይገድባቸው ከወጣቶች እኩል የሚተውኑ ናቸው፡፡ ሰዎችን በማስታረቅ እንዲሁም ባህልን በማስተዋወቅም ትኩረት የሚቸራቸው አዛውንት እንደሆኑም ይነገርላቸዋል። በሄዱበት ከብዙዎች ጋር ተስማምተው በመስራት ምስጋና የሚቸራቸው መሆናቸውን ከአካባቢው ሰዎች ሰምተናል፡፡ ታዲያ ይህንን ሁሉ ስንቅ የያዙትን አቶ ብርሃኑ ፍራንሲስ ማርሻ ለምን እንግዳችን አናደርጋቸውም፤ ብዙዎች ከርሳቸው የሚቀስሙት ጥሩ ተሞክሮ ይኖራል በማለት ለዛሬ የህይወት እንዲህ ናት አምዳችን እንግዳ አደረግናቸው። ስለዚህም ከእኝህ አዛውንት ብዙ የህይወት ልምድ ትቋደሱ ዘንድ እነሆ አልናችሁ።

ውልደትና እድገት

በጉራጌ ዞን እንድብር ከተማ የሴም የሚባል ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ በ1948.ም አዲስ ፍጥረት ወደዚህች ምድር ተቀላቀለ። በተለይ አባታቸው ፍራንሲስ ማርሻ እና እናታቸው ወለተወልድ ገብረማርያም የመጀመሪያ ልጃቸውን ስላገኙ በዚህ ልጅ መምጣት እጅጉን ተደስተው ነበር። ቤተሰቦቻቸው ምንም እንኳን በመካከለኛ ገቢ የሚተዳደሩ ቢሆንም፤ ለልጃቸውና ለቤተሰባቸው አያንሱም ነበር። እናም በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ስለሚያገለግሉ ልጃቸውን ከወለዱ በኋላ ይበልጥ ሥራቸውን ማጠናከር ጀመሩ። ምክንያቱም ለእርሳቸው የሚሆን ስንቅ በይበልጥ ማዘጋጀት ነበረባቸውና ነው።

አቶ ብርሃኑም ካደጉ በኋላ የአባታቸውን የሥራ ዘርፍ በመደገፍ የተቻላቸውን ያህል በመላላክና ማገዝ ባለባቸው ሁሉ ይረዱ ነበር። እንደማንኛም የገጠር ልጅም ከብት ጠብቀው አሳልፈዋል። በአካባቢያቸው አሉ ከሚባሉት እኩዮቻቸው መካከል የሚፈሩና የሚከበሩም ነበሩ። ምክንያቱም ሀይለኛ ስፖርተኛ በመሆናቸው ሳቢያ ብዙዎች ይፈሯቸዋል። ደፍሮ እርሳቸውን የሚናገር ሰውም አልነበረም። እንደውም በአካባቢው ልጆች ሲያጠፉ ተቆጥተውና ገርፈው የሚኮተኩቷቸው እርሳቸው እንደሆኑ ያስታውሳሉ። ልጅነት ለአቶ ብርሃኑ በእድሜ የገፋ አዛውንትነትም ነበር። ወላጆች እራሳቸው አልታዘዝ ያላቸው ልጅ ካለ እንደ ማስፈራሪያ ይጠቀሙባቸው እንደነበር አውግተውናል። እናም እንግዳችን ህጻን ሆነውም ለትልቁም ለትንሹም እኩል ታዛዥ ነበሩ። ኃይለኝነታቸውም በዚያው ልክ ነው።

አባታቸው ነጠላና ጋቢን በስፋት እያስመጡና ከሸማኔዎች እየተረከቡ ለማህበረሰቡ ያቀርቡ ነበርና በተለይ ሰው ሲሞት ከፈን የሚሆነውን ጨርቅ በስፋት በመሸጥ የታወቁ ናቸው። እናም ገንዘብ ያጠረው ሰው ከገጠማቸው «ከሞተ ሰው አልቀበልም፤ ካለው ሰው አካክሼ ችግሬን እፈታለሁ» በሚል አቋማቸው ይታወቃሉ። ታዲያም ልጃቸውን ሲያሳድጉም ለሰዎች ቅን እንዲሆኑ በማድረግ ነው። ማህበረሰቡ በዚህ ተግባራቸው እርሳቸውን ለየት አድርጎ እንዲወዳቸውም አድርገዋል። አቶ ብርሃኑ የአባታቸውን ባህሪ በስፋት የያዙ በመሆናቸው የተነሳ ምንም እንኳን በአካባቢው ልጆች ቢፈሩም ደግነት ግን ከውስጣቸው ያልተለያቸው እንደነበሩ ይናገራሉ።

እንግዳችን ብዙን ጊዜ ዘፋኝ መሆንንና በተለያዩ መድረኮች ላይ መተወንን አጥብቀው ከልጅነታቸው ይወዱታል፤ በዚህ ዘርፍም ተመርቀው ህይወታቸውን ሙሉ ማገልገል ይፈልጋሉም። ይሁን እንጂ ብዙም በዚህ ጉዳይ ሳይዘልቁበት ቆይተዋል። የማታ ማታ ሙያው ላይ በእስተርጅና የተሳተፉበት ቢሆንም።

የትምህርት ህይወት

አቶ ብርሃኑ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን መከታተል የጀመሩት እንድብር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። እስከ ስምንተኛ ክፍል ቆይተውበታል። በእዚህ ትምህርት ቤት ሚኒ ሚዲያ ታዋቂ የጥበብ ሙያ ያላቸው ስለነበሩ፤ በተዋናይነት፣ በክርክር፣ በግጥም ጸሐፊነትና አንባቢነት እንዲሁም በተለያዩ ስፖርታዊ ጨዋታቸዎች ልዩ ቦታ አግኝተው ነበር። ስለዚህም በስፋት የልጅነት ህልማቸውን ሲያከናውኑ ነው የቆዩት። በተለይም የማንኛውንም ሰው ገጸባህሪ ሸፍኖ በመጫወት የሚያህላቸው እንዳልነበር ያስታውሳሉ። እንደውም የሴት ገጸባህሪ ሲሰጣቸው የተለየ አድርገው ይተውኑት እንደነበር ይናገራሉ። ይህ ደግሞ የልጅነት ህልማቸው ነውና ትኩረት ይሰጡት ነበር።

ይሁን እንጂ ሰርቶ መለወጥን ቅድሚያ ስለሚሰጡ በቀድሞው አጠራር ጦር ሰራዊት ወይም በአሁኑ ወቅት መከላከያ ሰራዊት ተብሎ በሚጠራው ተቋም ውስጥ የስምንተኛ ክፍል ውጤታቸውን በማሳየት ተወዳድረው የጦር ኃይሉ የህክምና አገልግሎት ሰጪ ለመሆን ተመዘገቡ። ውጤቱም አሳለፋቸውና ስልጠና እንዲወስዱ ተደረገ፤ ከፍተኛ ውጤት በማምጣትም በዚያው ሰራዊቱን በማከም ሥራ ማገልገል ጀመሩ። ለ11 ዓመታት ያህልም በቦታው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሰሩ። በዚህ ሙያ ላይ እያሉ አማሬሳ በመሄድ ሥራቸውን ሲያከናውኑ ነበር። መቼም ሳይደግስ አይጣላ ነውና ነገሩ እዚህ ቦታ መምጣታቸው ሌላ ተጨማሪ እድልን አመቻችቶላቸዋል። ይኸውም ያቆሙትን የ9ኛና 10ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ አግዟቸዋል።

10ኛ ክፍል በኋላ ግን ትምህርታቸውን መከታተል አልቻሉም። ስለዚህም ለጊዜው አቋርጠውት ሥራቸው ላይ ብቻ ትኩረታቸውን አደረጉ።

የሥራ ሁኔታ

አቶ ብርሃኑ፤ ድሬደዋ፣ ሐረርና መሰል ከተሞች በመዘዋወርም ሥራቸውን ያጧጡፉት ጀመር። ያው ሙያቸው ህክምና በመሆኑ ቁስለኛ ባለበት ሁሉ ይገኛሉ፤ ፈውሳቸውንም ይለግሳሉ። እናም ይህ በእንዲህ እያለ ነበር በጣም አስቸጋሪ ፈተና ውስጥ የገቡት። ይኸውም ሶማሊያ ኢትዮጵያን በመውረሯ ወረራን ለመቀልበስ በተካሄደው ውጊያ ገብተው የወገን ሃይል እያከሙና እየደገፉ ሳለ እግራቸውንና ጭንቅላታቸውን በጥይት ተመቱ። ስለዚህም በዚያ ቦታ ሥራውን የመቀጠሉ ሁኔታ ተቋረጠ። በየወሩ ልክ እንደ ጡረታ 85ብር እየተከፈላቸውም እንዲቀመጡ ሆነ። ሥራቸውን ቢወዱትም በማይሆን አጋጣሚ ተለዩት።

እረፍት አልባው አቶ ብርሃኑ ከዚህ በኋላም ምንም እንኳን አካል ጉዳት የደረሰባቸው ቢሆንም በጡረታ ገንዘብ መቀመጥን አልወደዱትም። ስለሆነም ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ራሳቸውን አረጋግተው በዚያው በድሬደዋ ከተማ እርዳታ ማስተባበሪያ ውስጥ ኃላፊ ሆነው ተቀጠሩ። እርዳታው ለሶማሌ ህዝቦች እንዲደርስ በማድረግም ይሰሩ ነበር።

ይሁን እንጂ ኢህአዴግ ሃገሪቱን ሲቆጣጠር ከድሬደዋ ወጥተው ወደተወለዱባት ከተማ ተመለሱ። በቦታውም ሲደርሱ እርዳታ ማስተባበሪያው በየክልሉ እንዲሰራ ተደርጎ ነበርና አሁንም እርሳቸው ከዚሁ ሥራ ላይ ሆነው በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል እስከ 1990.ም ድረስ አገለገሉ። ከዚያ በኋላም በቦታው መስራትን ይፈልጉ ነበር። ሆኖም እርዳታ ይቁም ስለተባለ በዚህ ሙያ ላይ መስራታቸው ቆመና በወልቂጤ ከተማ ፍርድ ቤት ገብተው በአስተዳደር ዘርፍ ውስጥ መስራት ጀመሩ። ከአስተዳደር ዘርፉ ሲወርድ ጸሐፊነት፣ ከዚያ በመዝገብ ቤት ሃላፊነት፣ በፍትሀ ብሔር ችሎት ጸሐፊነትና በሌሎችም ዘርፎች እያሉ በዚሁ መስሪያ ቤት ውስጥ እየተዘዋወሩ አሁን ጡረታ እስከወጡበት ድረስ አገልግለዋል።

አቶ ብርሃኑ በወልቂጤ ከተማ ፍርድ ቤት ብቻ ለ17 ዓመት ያህል ሰርተዋል። ሐረር፣ድሬደዋና ሌሎች ከተማዎች ተዘዋውረው በእርዳታ ማስተባበሪያ ሲሰሩም ለ17 ዓመት ቆይተዋል። በአጠቃላይ አሁን እስካሉበት ዓመት ድረስ ለ45 ዓመት ያህል በመንግስት ሥራ ሲያገለግሉ ለዛሬው የጡረታ እድሜያቸው ደርሰዋል።

ጡረተኛው ሰራተኛ

አቶ ብርሃኑ ጉራጌ ዞን ከገቡ በኋላ በርካታ ተግባራትን ከውነዋል። ይሁንና ያው እድሜ ሲደርስ መድከም፣ መዘንጋት እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ የወጣቱን ያህል መልፋት ያዳግታልና በመንግስት መመሪያ መሰረት እረፍት እንዲያገኙ የጡረታ መብታቸው ተከብሮላቸው ጡረተኛ ሆነዋል። «እንቢ አላረጅም፤ ዛሬም ጉልበት አለኝ፤ በየመስኩ ተሰማርቼ እሰራለሁ፤ ከምንም በላይ የሚያንገበግበኝ ጡረተኛ ተብዬ ገንዘብ ከቤተሰቤ እየተቀበልኩ መኖር ነው። ስለሆነም በምችለው አቅም ዛሬም መስራትን እሻለሁ»የሚሉት አቶ ብርሃኑ፤ የልጅነት ህልማቸው ለማሳካት የተነሱት ጡረተኛ ከሆኑ በኋላ ነው።

«የተዋናይነት ተግባር ከወጣቱ እኩል በመስራት ማህበረሰቡን ያስተምራል፤ ስለዚህም እኔም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወርኩ የጉራጌን ባህል ከማስተዋወቅ ባለፈ ህልሜን ማሳካት ላይ እሰራለሁ፤ ለዚህም ደግሞ ሁሉም የጉራጌ ማህበረሰብ እያገዘኝ ይገኛል» የሚሉት እንግዳችን፤ ዛሬም ቢሆን በማያረጅ አንደበታቸው የጉራጌን አገርኛ ዘፈን ሲያዜሙ እውነትም ማርጀት የለባቸውም እንዲሉ ያስገድዶታል፤ ድምጻቸው ላይ ምንም አይነት የተለየ ዜማ አያዳምጡም፤ በፊታቸው ገጽታም እርጅና የተጫጫናቸው ሰው አይመስሉም። በተለይ ደግሞ የጉራጌኛ ሙዚቃ ተከፍቶ ሲጨፍሩ አጥንት ያለባቸው አይመስሉም። በእርግጥ እግራቸው ላይ ችግር አለባቸው፤ ይህንን ደግሞ የሚያውቁት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ነው። ይሁን እንጂ የሙዚቃው ምት ገና ሲጀምር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሲመለከቱ አጀብ ያሰኝዎታል። ትዕይንታቸውን ከተመለከተ አልታመሙም አውቀው ነው የሚልም ይጠፋል ብለን አናምንም።

እናም ጡረተኛው ሰራተኛ ካረጁም በኋላ ከባህልና ቱሪዝም መምሪያ ጋር በመሆን የተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ እየተገኙ ይሰራሉ፤ የተሰጣቸውን ገጸባህሪ በመሸፈንም ይተውናሉ። በዚህ ደግሞ ከተመጽዋችነት ድነው በራሳቸው ገንዘብ ያገኛሉ። ከዞኑም በመውጣት ባህሉን በመወከል ለባህሉ እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉም የሚገባቸውን ክፍያ ያገኛሉ። በዚህ ደግሞ ሁሌም ደስተኛ እንደሆኑና እስከህይወት ህልፈታቸው እንደሚሰሩበት ይገልጻሉ።

ገጠመኝ

የአራት ቋንቋ ባለቤት የሆኑት አቶ ብርሃኑ፤ በተዘዋወሩባቸው የአገር ውስጥ አካባቢዎች በርካታ ገጠመኞች እንዳሏቸው ይናገራሉ። ከእነዚህ መካከልም አንዱን እነሆ። ድሬደዋ ላይ ያገቧት ባለቤታቸው ነበረች ይህንን ገጠመኛቸውን እንዲፈጠር ምክንያት የሆነቻቸው። ይህም ገጠመኝ እንዲህ ነው። መቼም አደሬዎች አንዴ ከወደዱ ማንም ሰው ያንን ወንድ እንዲያይባቸው እድሉን አይሰጡም። እናም ባለቤታቸውም እርሳቸውን በጣም ትወዳቸው ነበርና ከማንም ጋር አብረው ሲሄዱና ያልተገባ ነገር ሲያደርጉ እንድታያቸው አትፈልግም።

ከእለታት አንድ ቀን ታዲያ እርሳቸው በባህሪያቸው ከሁሉም ሰው ጋር ተጨዋች ስለነበሩ ከመስሪያ ቤት ሴት ባልደረቦቻቸው መካከል ሆነው እየተሳሳቁ ሲጓዙ አየቻቸው። ድምጽ ሳታሰማም ከኋላቸው በመሆን ትከታተላቸው ጀመር። በጊዜው በሚናገሩት ንግግር በጣሙን ተናዳለች፤ ይሁንና ማስደንገጥም ሆነ መናገር ግን አልፈለገችም። ስለዚህም ንዴቷን ዋጥ አድርጋ እስከገቡበት ቤት ድረስ ተከታተለቻቸው። እነርሱ ቤት ውስጥ ሲገቡ እርሷ ወደ ቤቷ ተመልሳ ባለቤቷ እስኪመጡ ድረስ ትጠባበቃቸው ጀመር።

የተያዘው መርሃግብር አልቆም በስተመጨረሻ ማታ እቤት ሲገቡ ውሏቸው ምን እንደሚመስል ትጠይቃቸዋለች። እርሳቸውም «እንደተለመደው ነው» የሚል ምላሽ ይሰጧታል። ከዚያ እራታቸውን በሚገባ ከመገበችና የሚያስፈልጋቸውን ነገር ከሰጠች በኋላ ማረፊያቸው ሲደርስ ወደ ጓዳ ገብታ መጥረቢያ ይዛ በመምጣት እንዲህ ስትል ትናገራቸዋለች «ብርሃኑ እኔ ላንተ አንሼ ነወይ 44 ሴት እያንጋጋህ በየመንገዱ የምትገለፍጠው፤ ስለዚህ ከዚህ በኋላ እንዲህ ስታደርግ ባይህ በተኛህበት በዚህ መጥረቢያ ቅንጥስ አድርጌ ነው የምጥልህ»አለቻቸው።

ከዚህ በፊት አንድ ጓደኛቸው እንዲህ እንደርሳቸው ገጥሞት እንደተጎዳ ስላስታወሱ እርሳቸው ላይ እንዳይሆን ይጸልዩ እንደነበርና ከእርሷ ውጪ ምንም ማድረግ እንደማይፈልጉ በተብረከረከ ጉልበታቸውና ትንፋሽ ባጠረው አንደበታቸው እንደተማጸኗት ያስታውሳሉ። ስለዚህም ይህንን ገጠመኛቸውን እንደማይረሱትና የሁልጊዜ ትዝታቸው እንደሆነ አውግተውን የእርሷ ይህንን ማድረግም ከእርሷ ቀጥለው ላገቧቸው ሚስቶች አክብሮትና ፍቅር እንዲኖራቸው እንዳደረጋቸው ገልጸውልናል።

ፈተና

1969 .ም ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ከጅግጅጋ በታች በቁጥጥር ሥር በዋለችበት ጊዜ ነበር ይህ የማይወጡትና በህይወታቸው እስካሁን ድረስ ፈተና የሆነባቸው ችግር የገጠማቸው። ይህ ጊዜ እኔ የተመታሁበት፣ በዚያው ልክ ደግሞ በሞግዚትነት አሳድጋት የነበረው የሁለት ዓመት ህጻን ተማርካ የተወሰደችበትና ሰባት ቀን ሙሉ ምግብ የሚባል ነገር ባፌ ሳይዞር ቅጠል፣ አፈርና ጭቃ እየበላሁ ህይወቴን ያቆየሁበት ነበር ይላሉ።

የርሀብን ምንነትን ያየሁበትና በደቂቃ መግደል እንደማይችል የተረዳሁት ጊዜ ነው። ምክንያቱም በወቅቱ አስተዳድረው የነበረውም ግምጃ ቤት በመድፍ ድምጥማጡ ጠፍቷል። አንዲት ፍሬ እህል እንኳን በአካባቢው የለም ነበር። ስለዚህም ይህ ወቅት ጓደኞቼን፣ ልጄን፣ ዜጎቼን ያጣሁበት በመሆኑ መሪር ሀዘን የተሰማኝ ወቅት ነበር። መቼም ትረፊ ያላት ነፍስ ነችና በሰባት ቀናችን ጅግጅጋ ለመግባት በመብቃታችን ህይወታችን ሊተርፍ ችሏል። እናም ይህ ወቅት በህይወቴ እጅግ ከባድና አሰቃቂ ነገሮችን ያሳለፍኩባቸው ጊዜ ስለነበር ፈታኙ ወቅት ስል አስታውሰዋለሁ ብለውናል።

የቤተሰብ ሁኔታ

አቶ ብርሃኑ በተለያዩ ሥፍራዎች እየተዘዋወሩ የሰሩ በመሆናቸው ምክንያት ኑሮውን ለመቋቋምና ለማሸነፍ ሲሉ በየሄዱበት ባለቤት የምትሆናቸው ሴት ያገቡ ነበር። እናም በርካታ ሚስቶች ነበሯቸው። በቁጥርም 11 እንደሚደርሱ በወጋችን መካከል ነግረውናል። ከእነዚህ 11 ሚስቶቻቸውም 44 ልጆችን አፍርተዋል። ይሁንና ዛሬ ላይ ከአንዷ ባለቤታቸው ጋር ነው በፍቅር አብረው የሚኖሩት። ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው በቤተሰብም ሆነ በማህበረሰቡ ዘንድ ብዙ ሴት ማግባት አይፈቀድም፤ ከማህበረሰቡም ያስገልላል። ስለዚህም እርሳቸውም አሁን ያገቧትን ባለቤታቸውን ይዘው የማህበረሰቡን ወግና ባህል አክብረው ይኖራሉ።

ከአገቧቸው 11 ሚስቶቻቸው ውስጥ 10 በሕይወት እንዳሉ የሚያስረዱት አቶ ብርሃኑ፤ ከሁሉም ጋር በፍቅርና በመተሳሰብ እንደሚኖሩ፣ ሁሉም ልጆቻቸውም በተለያየ መልኩ መጥተው እንደሚጠይቋቸው፤ ካልተመቻቸው ደግሞ አባታቸውን ይደግፋል ብለው የሚያስቡትን ነገር እንደሚያደርጉ ይናገራሉ። አብዛኞቹም በውጪ አገር የተለያየ ሙያ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ስለሆኑ ምንም እንኳን አገር ውስጥ ባይመጡም ከዚያ ሆነው እንደሚደግፏቸውና በጣምም እንደሚወዷቸው አውግተውናል።

በባህሉ ዘንድ ተገቢ ያልሆነ ተግባር እስካሁን ስፈጽም እንደነበር ይሰማኛል ይሁንና ኑሮን ለማሸነፍ በተለይ ለወንድ ልጅ ከባድ ነውና እድርጌዋለሁ። ይህ የሆነው ደግሞ በተለያየ አጋጣሚ ስለነበር በጣም ደስተኛ ነኝ። 44 ልጆችም ስላሉኝ ዛሬ ላይ በህይወቴ ደስተኛ እንድሆን አድርጎኛል።» የሚሉት እንግዳችን፤ «ልጅ በእድሉ ያድጋል» የሚለው አባባል እኔ ጋር ሰርቷል። ምክንያቱም ያገበኋቸው ሴቶች ብዙም የሚያስቸግሩና ለልጆቻቸው የማይሰሩ አልነበሩም። እናም ምንም እንኳን እኔ የማግዘው ነገር ቢኖርም በይበልጥ ግን ልጆቹን በመንከባከብና ለቁም ነገር እንዲበቁ በማድረጉ ዙሪያ የእነርሱ ኃላፊነት ከፍ ያለ ነበር ልጆቼ ትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ ሆነዋል።

ዛሬም ላይ ልጆቼ እንደወደዱኝና አባትነቴን እንደተቀበሉ እንዲቀጥሉ አድርጓቸዋል። በቤተሰብ ሕይወታቸው ደስተኛ የሚሆኑ ሰዎችም እንዲፈጠሩ ያስቻላቸው ለሁሉም ካለኝ ክብርና ችሮታ አኳያ ነው። ስለዚህም ምንም እንኳን ከባህሉ የወጣ ተግባር ብከውንም ዛሬ ላይ ለመጣው ሕይወቴ ግን ፈር ቀዳጅ የሆነ መስመር እንዲኖረኝ እድሉን አመቻችቶልኛል፤ አስተምሮኝም አልፏል» ይላሉ።

የቀጣይ እቅድ

ልጆቻቸው «ይህንን ዓመት ሙሉ ለፍተህ አሳድገኸናል፤ በብዛትም በርከት ያልን ነን፤ ስለዚህ አሁን አርፈህ ተጦር፤ ምንም መስራት የለብህም» ይሏቸዋል። እርሳቸው ግን ሰርቶ ማግኘትና ከሌሎች ተቀብሎ መኖር እኩል እርካታ የለውም የሚል አስተሳሰብ ያላቸው ስለሆኑ በላባቸው ሰርተው ማደርን ይመርጣሉ። ሁሌ ተመጽዋች መሆን ደግሞ ሰነፍ ያደርጋል፤ የሥራ ፍላጎትንም ይገድላል ብለው ስለሚያምኑ ሁልጊዜ የሚያረካቸውን ሰርተው የማግኘት ተግባር ላይ እንደሚሰማሩ ይናገራሉ። ገንዘብና የቀጣይ እቅዳቸውም ህይወታቸው እስኪያልፍ ድረስ ሰርተው በሚያገኙት ገንዘብ መኖር እንደሚፈልጉ ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ «አገሬ ከእኔ የምትፈልገውን ነገር ሁሉ ማድረግን እሻለሁ። በተለይ በተለይ የጉራጌ ባህል እንዲተዋወቅ በማድረጉ ዙሪያ በይበልጥ የምሰራ ይሆናልም» ብለውናል። መቼም ጊዜና ይዘታችን እንዲሁም አምዱ የሚይዘው ብዛት ይወስነናል እንጂ ስለእንግዳችን ብዙ ነገር ማለት ይቻል ነበር። ይሁንና ከብዙ በጥቂቱ ካላቸው ተሞክሮ ዋና ዋናዎቹን ለማሳየት ሞክረናልና ፅሁፋችንን እዚሁ ላይ እንቋጭ።

 

ጽጌረዳ ጫንያለው

Published in ማህበራዊ

የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በህገ መንግስቱ መሰረት የተሰጠው ሥልጣንና ተግባር እጅግ ከፍተኛ ስለመሆኑ የኢፌዴሪ ህገ መንግስትን 55ኛ አንቀፅ ማንበብ ብቻ በቂ ነው፡፡ ህግን የማውጣትና ሹመቶችን የማጽደቅ ኃላፊነቱ ምንም እንኳን በህግ የተገደበ ቢሆንም የምክርቤቱ የስልጣን ደረጃ ወይንም ልዕልና ምን ያህል ላቅ ያለ ስለመሆኑም ከዚህ አንቀፅ ድንጋጌዎች ላይ መረዳት ይቻላል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሶስተኛ ዓመት የስራ ዘመኑን በወሩ ማገባደጃ ይጀምራል። በዘንድሮው የስራ ዘመኑ እንደ ወትሮው ሁሉ አስፈጻሚ አካላትን የመከታተል ፣የመንግስት ህግና ደንቦችን የማውጣት እንዲሁም መመሪያዎችን የማዘጋጀትና የማጽደቅ ስራውን ይሰራል ተብሎ ብቻ አይጠበቅም። ይልቁንም ከተለመደው በተለየ አገሪቱ አሁን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚሄዱ አዳዲስ ስራዎች ይኖሩታል። ትልልቅ ውሳኔዎችን፣ አደረጃጀቶችንና ሌሎች ተግባራትን ያከናውናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።በ ተለይ ደግሞ በተጠናቀቀው በጀት አመት የተጀመረው የፀረ ሙስና ትግል ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትልቅ ስራ ይጠብቀዋል፡፡ በተጨማሪም በአዋሳኝ ድንበሮች አካባቢ የሚታዩ ግጭቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ ስራዎች ይጠብቁታል፡፡

አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የህግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው፡፡ እንደሳቸው አባባል፤ ምክር ቤቱ ከእረፍት ሲመለስ ቋሚ ኮሚቴዎች የሚከታተሏውን መስሪያ ቤቶች የፀረ ሙስና ትግሉን በተጠናከረ መንገድ እንዲሰሩና እንዲያስቀጥሉ መመሪያ ይሰጣሉ። በዚህም ረገድ በተጠናቀቀው በጀት አመት የተጀመረ ስራ አለ፡፡ ይህ በህጋዊ መንገድ ዳር እንዲይዝና አስተማሪ የሆነ ውሳኔ የሚያገኝበት በተጨማሪም ደግሞ የሚሰራው ስራ የህግ የበላይነትና ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ መልኩ እልባት እያገኘ እንዲሄድ የፍትህ አካላቱ ይህንን ጠብቀው የተፋጠነ ውሳኔ እንዲሰጡ የማጠናከር ስራ ይሰራል።

በሌላ በኩል እነዚህ ስራዎች ይዘው የሚንቀሳቀሱት ተቋማት በተለይ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ህብረተሰቡን የማስተማር ስራውን በተለይ የሙስናን አስከፊነት ህብረተሰቡ በሚገባ እንዲረዳው ከዚህ ቀደም የጀመሩትን እንዲቀጥሉ የመደገፍና ማገዝ ስራ ምክር ቤቱ ይሰራል፡፡ በዋናነት የሚፈለገው የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ነው፡፡ በተለይ በህብረተሰቡ ዘንድ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› የሚለውን አባባል የሚፀየፍ ማህበረሰብ ለመፍጠር በጋራ እንደሚሰራ አቶ ጴጥሮስ ይናገራሉ፡፡

አገልግሎት ለማግኘት የማይገባ ጥቅም መክፈልም ሆነ መቀበል እንዲሁም መብታቸውን የሚጠይቁ ሰዎች የራሳቸውን ግዴታ ተወጥተው አግባብ በሆነ መንገድ በህግ በተፈቀደላቸው መንገድ ማግኘት እንደሚችሉ ግንዛቤ ለመስጠት እቅድ ተይዟል፡፡ አገልግሎት የሚሰጠው ክፍል በተፈቀደለትና በተቀመጠለት ህግ መሰረት ያንን ህግ አክብሮ አገልግሎት መስጠት ምንም ተጨማሪ ነገር ሳይጠይቅ ግልፅ በሆነ መንገድ የሚሰራበት አካሄድ በቁጥጥርና በክትትል ወቅት በአካልም ጭምር በሚደረግ ክትትል እንዲረጋገጥ በአግባቡ ለመስራት መታሰቡን ሰብሳቢው ይናገራሉ፡፡

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ የአዋሳኝ አካባቢዎች ህብረተሰቡ ተዋዶ ተዋልዶ የሚኖርባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ ካለው ትስስርና የህብረተሰቡ አኗኗር አንፃር ሲታይ አዋሳኝ መስመር መቀመጥ አለበት የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ህብረተሰቡ ተቀላቅሎ ነው የሚኖረው፡፡ በአካባቢው የተለያዩ አካላት ጣልቃ እየገቡ የሚያደርጉት ትንኮሳ ጋር በተያያዘ የሚጋጩበት ሁኔታ አለ፡፡ አሁን የምናየው ከዛ ጋር የሚያያዝ ስለሆነ እነዚህ ነገሮች በተቻለ ሁኔታ በፍጥነት ተፈተው በህብረተሰቡ ውስጥ የነበረው አንድነትና ትስስር የበለጠ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ስራ መስራትና ችግሩን በማባባስ በኩል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ካሉ እነዛን ለይቶ ለህግ የሚቀርቡበትን መንገድ ምክር ቤቱ እንደሚያከናውን አቶ ጴጥሮስ ያስረዳሉ፡፡

የመላው ኢትዮጵያ ብሄራዊ ንቅናቄ (መኢብን) ፕሬዚዳንት አቶ መሳፍንት ሽፈራው እንደሚሉት፤ በቅርቡ በሚከፈተው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋሳኝ ቦታዎች ላይ የሚታዩ ግጭቶች መፍትሄ ለውይይት መቅረብ አለበት፡፡ ምክንያቱም ህብረተሰቡ ውስጥ እየተብላላ ያለና ጊዜ እየጠበቀ የሚፈነዳ ነገር ነው፡፡ ጉዳዩ ጊዜያዊ መፍትሄ እየተሰጠው አይደለም፡፡ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ በመጀመሪያ ደረጃ የችግሩ ምንጭ ምንድነው? ችግር ፈጣሪዎቹ እነማን ናቸው? ለረጅም አመታት አብሮ በጉርብትና የኖረ ህዝብ ለግጭት ያነሳሳው ነገር ምንድነው? በችግር ውስጥ የክልሉ መንግስታት አሉበት ወይስ የሉበትም? የሚለውን ጉዳይ መታየት አለበት፡፡ ጉዳዩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ እንደ ዋና ጉዳይ መነሳት አለበት፡፡ ምክንያቱም የሁለቱ ክልሎች ተወካዮች በምክር ቤቱ መቀመጫ አላቸው። እነሱም ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ መስራት አለባቸው፡፡ ችግሩን ሊፈታ የሚችል ውይይት እንዲደረግ ምክር ቤቱ ተግቶ መስራት አለበት፡፡

በፀረ ሙስና ትግሉ የተጀመረው ስራ የሚበረታታ ነው፡፡ በተጋጋለና ሁሉን ባማከለ መንገድ መቀጠል ይገባል፡፡ ሙስና እንደሚታወቀው በቀጥታ የሚደረግ አይደለም። በተዘዋዋሪ መንገድ ነው የሚሰራው። መንግስት የጀመረውን የሙስና ትግል አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ሙሰኞች ላይ ጥቆማ የሚያደርጉ ሰዎች የህግ ከለላ ሊሰጣቸው ያስፈልጋል፡፡ የፀረ ሙስና ትግሉም በዚሁ ልክ እንዲቀጥል ምክር ቤቱ ትልቅ የቤት ስራ እንዳለበት አቶ መሳፍንት ይገልፃሉ፡፡ በቅርቡ በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የሚገኙትን ጉዳዩን እየተከታተለ ያለው ጠቅላይ አቃቤ ህግ የተጠናከረ ስራ እንዲሰራም ምክር ቤቱ ድጋፍ ማድረግ አለበት፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና በመንግስት ስራ የተሰማሩት አቶ ይድነቃቸው ሁሉአለም እንደሚናገሩት፤ ምክር ቤቱ ሁሌም በየዓመቱ ወቅቱን ጠብቆ ይከፈታል። ሆኖም በአዲሱ ዓመት የስራ ዘመኑ ግን ለየት ያለ ተግባርን መፈጸም ይኖርበታል። በተለይም በተጀመረው የፀረ ሙስና ትግልና በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚታዩትን ግጭት ለመፍታት መድረክ የሚያመቻች መሆን አለበት።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት በዋናነት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የህዝብ ጥያቄዎች ተበራክተዋል። እነዚህን ደግሞ በህገ መንግስቱ መሰረት የሚመለሱበትን መንገድ ማመቻቸት አለበት። በሌላ በኩል ምክር ቤቱ ዓመቱን በሙሉ በሚያደርገው ስብሰባ ላይ የህዝብን ጥያቄ አንስቶ መወያየት፣ የመልካም አስተዳደር በደሎች እልባት የሚያገኙበትን ብሎም ዜጎች በአገራቸው ሀብት እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲኖር መወያየት ይኖርበታል። በቀጣይ ጊዜያቱ ይህንን ያደርጋል የሚል እምነት አላቸው።

በአንዳንድ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ የሚታዩ የአሰራር ስህተቶች እንዲሻሻሉ ምክር ቤቱ የራሱን ሚና መጫወት እንዳለበት የሚጠቅሱት አቶ ይድነቃቸው፤ ምክር ቤቱ በሚያደርጋቸው የቁጥጥር ስራዎች ላይ የሚያገኛቸውን ስህተቶች ታርመው ህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ ጠንክሮ የሚሰራበት ዘመን መሆን እንዳለበት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡

የምክር ቤቱ አባላት የእረፍት ጊዜውን ጨርሰው ሲመለሱ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በመመልከት በተለይ በፀረ ሙስና ትግሉና በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ አካባቢ የሚታዩ ችግሮች የሚፈታበት መንገድ ላይ ውይይት ማድረግ እንዳለበት ወጣት ነብዩ አያሌው ይናገራል፡፡ በተለይ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ጉዳት ስለደረሰባቸው የሚቋቋሙበት መንገድ ሊፈለግ እንደሚገባም ይጠቅሳል፡፡

በሌላ በኩልም የፀረ ሙስና ትግሉ ባለበት እንዲቀጥል ሙስና የሰሩ ሰዎች ምክር ቤቱ በሚያደርገው የክትትልና ቁጥጥር ስራው በቁጥጥር ስር መዋል እንዳለባቸው ይገልፃል፡፡በተጨማሪም ምክር ቤቱ የሚቆጣጠራቸው መስሪያ ቤቶች የአሰራር ክፍተታቸውን አሟልተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ የተጠናከረ ስራ መስራት እንዳለበትም ያስረዳል፡፡

መሻሻል ያሳዩ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ሌሎችም የአሰራር ስልቱን በመጋራት ለህዝብ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ምክር ቤቱ የክትትልና ቁጥጥር ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይጠቅሳል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በተለይ በወረዳዎች ላይ የሚታዩ የአሰራር ክፍተቶች ለሙስና በር እየከፈቱ በመሆናቸው ትኩረት ሊሰጥባቸው እንደሚገባ ያሳስባል፡፡

 

መርድ ክፍሉ

 

Published in ፖለቲካ

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት(....) 2009 በጀት አመት በባህር ትራንስፖርትና የወደብ አገልግሎት የተለያዩ ስራዎችን አከናውኗል፡፡ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ የድርጅቱን የስራ አፈፃፀምና የተያዘውን በጀት አመት እቅድ በተመለከተ ሰሞኑን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸውም ድርጅቱ በተጠናቀቀው በጀት አመት ከወደብ ላይ እቃዎችን በመልቲ ሞዳል አገልግሎት ቀልጣፋ አገልግሎት ቢሰጥም የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ግን ፈተና ሆኖበት እንደነበር ገልፀዋል፡፡ በተያዘው በጀት አመት ድርጅቱ የአገልግሎት ደረጃውን በማሳደግ የእቃ ወደብ ላይ ቆይታን ለማሳጠር እቅድ መያዙንም አመልክተዋል፡፡

የወደብ ጭነት አገልግሎት

የወደብ ትራንስፖርት አገልግሎት በ2009 በጀት አመት ቢታይ የራሱንና የኪራይ መርከቦችን በመጠቀም ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን በላይ ገቢ እቃ አጓጉዟል፡፡በጭነት ማስተላለፍ አገልግሎት ከ179 ሺ ኮንቴነር በላይ ገቢ ጭነቶችን ተስተናግደ ዋል፡፡ዘጠኝ ሺ 500 ተሸከርካሪ ገቢ ጭነቶች በመልቲ ሞዳል ስርአት ወደ አገር ውስጥና የጉምሩክ ፈቃድ ባላቸው መጋዘኖች ተጓጉዘዋል፡፡ እንዲሁም በነጠላ ትራንስፖርት ዘዴ ከ2 ነጥብ አራት ሚሊዮን ቶን በላይ ገቢ ጭነት የማስተላለፍ አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ቢታይ በተመሳሳይ ወደ 290 ሺ ቶን እንዲተላለፉ ተደርጓል፡፡

ከገቢ አንፃር ድርጅቱ ለሰጠው አገልግሎት 15 ነጥብ 811 ቢሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል፡፡ከዚህ ውስጥ ትርፍ ከታክስ በፊት አንድ ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር ያገኘ ሲሆን የተጣራ ትርፉ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር አስገብቷል፡፡ ከፕሮጀክት አፈፃፀም አንፃር ሲታይ ድርጅቱ የወደብ ማስፋፋት በራስ አቅምና በመንግስት የበጀት ድጋፍ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ከዚህም ውስጥ በሞጆ ደረቅ ወደብና በድሬዳዋ ደረቅ ወደቦች የሚደረጉት የማስፋፊያ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በቀጣይም ከባቡር ጋር ደረቅ ወደቦችን የማገናኘት ስራዎች በቀጣይ ይከናወናል፡፡ ነገር ግን በፕሮጀክት አፈፃፀም ላይ በርካታ ውስንነቶች አጋጥመውታል፡፡ እነዚህን ውስንነቶች ለመፍታትም ቀሪ ስራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ለመስራት በተያዘውት በጀት አመት እቅድ ውስጥ አካቶታል፡፡

በባቡር መሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ ባቡሩን ከወደብ ጋር ለማያያዝ ስራዎች ተጀምረዋል፡፡ጊዜያዊ ባቡር የመጫኛ ቦታ ጅቡቲ ላይ ተዘጋጅቷል፡፡ ጅቡቲ በሚገኘው የኮንቴነር ተርሚናል አካባቢ መጫኛ ተዘጋጅቶ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል፡፡ ከውጭ የመጣውን ኮንቴነር አገር ውስጥ ካሉ ደረቅ ወደቦች ጋር ከማገናኘት አንፃርም የሞጆ ደረቅ ወደብ ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህ ረገድ ባቡሩን ከወደብ ጋር የማገናኘት ስራዎች እየተጠናቀቁ ናቸው፡፡

የወደብ ቆይታ

የእቃ የወደብ ላይ ቆይታ በተለይ የጅቡቲ ወደብ ቆይታ በመልቲ ሞዳል ከአስር ቀን በታች ነው፡፡በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የታሰበው ሶስት ቀን ለማድረስ ነው፡፡ ቀኑን መቀነስ ይቻላል፡፡በተወሰኑ ሰነዶች ብቻ በመልቲ ሞዳል አገልግሎት ኮንቴነርና ገቢ ተሽከርካሪዎች ማንሳት ይቻላል፡፡በተጨማሪም ብረትና ሌሎች የኮንስትራክሽን እቃዎች እንዲሁም እየተነዱ የሚመጡ ተሽከርካሪዎችን በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ስርዓት ትግበራ ውስጥ እንዲገቡ ከተደረገ በተመሳሳይ እቃዎች ወደብ ላይ ሊቆዩ የሚችሉበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡

በዩኒ ሞዳል አገልግሎት ግን ረጅም ጊዜ እቃዎች ወደብ ላይ የሚቆዩበት ሁኔታ አለ፡፡ እቃዎች ወደብ ላይ የሚቆዩት በዩኒ ሞዳል የሚስተናገዱ እቃዎች ከወደብ ላይ ለማንሳት ሰነድ ክፍያ የሚከናወነው እዛው ወደብ ላይ በመሆኑ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በዋናነት በጭነት ባለቤቱ አስፈፃሚነት ወይም እሱ በሚመድበው ተወካይ አስፈፃሚነት የሚመራ ነው፡፡ በሌላ በኩልም በእቃ ተቀባዩ ትኩረት ማነስ መሟላት የሚገባቸው በወቅቱ አለመቅረብ፣ የትራንስፖርት አቅርቦት እንዲሁም የጉምሩክና የወደብ አሰራር ስርዓት የሚወስደው ጊዜና የክፍያ ሁኔታ ተደማምሮ እቃዎች እስከ አርባ ቀን ወደብ ላይ ይቆያሉ፡፡

አብዛኛው በወደቦች ላይ ተቀምጠው የሚታዩት የመንግስት ጭነቶች ናቸው፡፡ ከፍተኛውን የያዙት እነሱ ናቸው፡፡11 416 ኮንቴነሮች በበጀት አመቱ መጨረሻ ላይ ወደብ ላይ ነበሩ፡፡ከዚህም ውስጥ 10674 የግል አስመጪ ንብረቶች ናቸው፣335 የመንግስት ተቋማት ያስመጧቸው ኮንቴነሮች ናቸው እንዲሁም የልማት ድርጅቶች 470 ኮንቴነሮች ናቸው፡፡ ለነዚህ ኮንቴነሮች ወደብ ላይ መቆየት በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የቅልጥፍና ችግር፣እቃውን ያስመጡት በወቅቱ አለማንሳት እንዲሁም የአሰራር ክፍተቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ለዚም ችግር መፍትሄነት የመልቲ ሞዳል ስርዓት በማስፋፋት ወደብ ላይ እቃዎች ብዙ ቀናት እንዳይቆዩ የማድረግ ስራዎች በእቅድ ተይዘዋል፡፡

ያጋጠሙት ችግሮች

በበጀት አመቱ እንደ ችግር የሚጠቀሱት የመጀመሪያው በአገር አቀፍ ደረጃ የፖሊሲና ስትራቴጂ የአፈፃፀም ውስንነት ሎጂስቲክሱ የሚመራበት የተቀናጀና የተደራጀ ፖሊሲና ስትራቴጂ ችግርና ከህግና መመሪያ ማዕቀፍና አሰራር አንፃር ያልተሟሉ ስራዎች ነበሩት፡፡ የተሟሉትም ቢሆንም የአፈፃፀም ጥሰቶች ተስተውለውባቸዋል፡፡ የንግድ ስርዓቱ በራሱ የሚፈጥረው ችግርና አንዲሁም የተቋማት የቅንጅት ችግሮችም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከውስጥ አሰራር አንፃር የድርጅቱ አደረጃጀትና አሰራር የራሱ ውስንነቶች አሉበት፡፡ የማኔጅመንት አቅሙ ከሚጠበቀው ዘርፍ የሚጠበቀው ያክል አለመሆን እንደ ችግር ታይቷል፡፡ ይህን ተከትሎ ለኪራይ ሰብሳቢነት ተጋላጭ የሚያደርጉ በርካታ ስራዎች ለመስራት ተችሏል፡፡ በቴክኖሎጂ ረገድ ዘርፉ የሚመራበት በአለም አቀፍ ደረጃ የሚመራበትን ያክል በተለይ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እገዛ አለመኖሩና አሰራሩ ኋላ ቀር መሆኑ ፈታኝ ጉዳይ ነበር፡፡

ከመርከቦች ጋር የተያያዙ ችግሮች ውስጥ አንደኛው የቴክኒክ ችግር ነው፡፡ ከችግሮቹ መካከል መርከቦች በብልሽትና ያለስራ መቆም ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም መርከቦቹ የሚሰማሩበት የንግድ ጉዞ አዋጭነት እና ታሪፍ ጭምር በድጋፍ ሆነ በሚሸከሙት ጭነት መጠን የተነሳ ኪሳራ አለባቸው፡ ፡ሌላኛው ደግሞ የማኔጅመንት አቅም ማነስ ምክንያት የራሱ መርከቦቹ የታሰበላቸውን አላማ እንዲያሳኩና በብቃት እየተመሩ አዋጭ ሊሆኑ በሚችሉ የንግድ መስመሮች ላይ እየተሰማሩ ወጤት እያመጡ አይደለም፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነት ስጋትና ተጨባጭ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች በዋነኝነት የሚታዩ ናቸው፡፡ እንዲሁም ከራስ መርከቦች ጋር በተያያዘ እንደሚታ ወቀው ድርጅቱ የባህር ትራንስፖርት የሚሰጠው በራሱ የተወሰነ መርከብና ከሌሎች መርከቦች ቦታ በመከራየት እቃዎች የማጓጓዝ ስራ ይሰራል ፡፡ መርከብ ተከራይቶ የሚሰጠው አገልግሎት ትርፋማ ቢያደርገውም በራሱ መርከብ ግን ውጤት አላመጣም፡፡

መንግስት በአገር አቀፍ ደረጃ የፀረ ሙስና ትግል እያደረገ ይገኛል፡፡ በድርጅቱም የተጠረጠሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር ይገኛሉ፡፡በድርጅቱ ያለው የአሰራር ስርዓት ክፍተት መኖር ለኪራይ ሰብሳቢዎች በር መክፈቱን ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ ድርጅቱ አገልግሎቱን በተረጋጋ ሁኔታ እያከናወነ ይገኛል፡፡

የተያዘው በጀት አመት እቅድ

የወደብ ትራንስፖርት አገልግሎት በተመለከተ በተያዘው በጀት አመት 189 899 ኮንቴነሮች፣17944 ተሽከርካሪዎች፣257 966 ቶን ብረት በመልቲ ሞዳል ስርዓት ወደ አገር ውስጥ ወደቦችና የጉምሩክ ፈቃድ ያላቸው መጋዘኖች ለማጓጓዝ እቅድ ይዟል፡፡ በተጨማሪም 320778 ቶን ወጪ ጭነት ለማስተላለፍ አቅዷል፡፡

በወደብና ተርሚናል አገልግሎት ዘርፍ 180 ሺ ገቢ ሙሉ ኮንቴነሮች እና 17 944 ተሽከርካሪዎች ለማስተናገድ ያቀደ ሲሆን ለ235123 ቶን ጭነት ከመርከብ አገልግሎትና 128522 ቶን የዝግ መጋዘን አገልግሎት ለመስጠት አቅዷል፡፡ የወደብ ቆይታን ከመቀነስ አንፃር የመልቲሞዳል ኮንቴነር የጅቡቲን ቆይታን ወደ አምስት ቀን እንዲሁም የጥቅል እቃና የብረት ጭነት ቆይታ ወደ 15 ቀን ለማድረስ እቅድ ተይዟል፡፡

በአጠቃላይ ድርጅቱ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች 23 ነጥብ605 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ያቀደ ሲሆን፤21 ነጥብ 614 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ አንድ ነጥብ 991 ቢሊዮን ብር ትርፍ ለማስገባት አቅዷል፡፡ ድርጅቱ ለመሰረተ ልማት ማስፋፊያ እና ለግዥዎች የፋይናንስ ምንጩን አራት ነጥብ 033 ቢሊዮን ብር ከተጠራቀመው የድርጅቱ ትርፍ፣ ከአገር ውስጥ ባንክ ብድር ሲሆን አንድ ነጥብ 101 ቢሊዮን ብር ደግሞ የውጪ ብድር ይሆናል፡፡

 

መርድ ክፍሉ

Published in ኢኮኖሚ

በቡድኑ ጥቃት በህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው፤

 

በሶሪያ አብዛኛው የሶሪያ ዴሞክራቲክ ኃይል የወከለውና በፒኬኬ (የኩርዲስታን ሰራተኞች ፓርቲ) የተፈጠረ ቡድን አለ።ይህ ቡድን የሰዎች ጥበቃ ክፍሎች በሚል የሚታወቀው ዋይ ፒ ጂ ነው። በምዕራባውያን ፖለቲካዊ ድጋፍ እንዳለው ይገለፃል። ከምዕራባውያን አርበኞችና የጦር አዛዦች በአገኙት እውቅናና በሰበሰቡት በርካታ ድጋፍ በርካቶች ከቡድኑ ጋር ተሰልፈዋል፡፡

ወጣትና ሴት ወታደሮችን እንደ ሽምቅ ተዋጊ መጠቀም የቡድኑ ስልት ነው።ከዳዕሽ ጋር በሚፋለሙበት ጊዜ ፒኬኬ ሚዲያውን የእነዚህ ወጣትና ቆንጆ ሴቶች ፎቶ ‹‹የነጻነት ታጋዮች›› በማለት ዝናን የማስገኛ አድርገዋቸው ነበር፡፡ እነዚህ ለማስታወቂያነት ከሚጠቀሙባቸው የዋይ ፒ ጂ ሴቶች ገሚሶቹ ከወንድ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን በአሜሪካ መሪነት በሶሪያ ዴሞክራቲክ ኃይል ይፋለማሉ፡፡

ስቴፈን ጎዋንስ የተባሉ ጸሐፊ ‹‹ዘ መይዝ ኦፍ ዘ ኩርዲሽ ዋይ ፒ ጂስ ሞራል ኤክሰለንስ›› በሚል ፅሑፋቸው፤ በሶሪያ የፒኬኬ ዓላማ በሰሜናዊ ሶሪያ ግዛት የአረብ ሙስሊሞች በስፋት በሚገኙባት በራስ ገዝነት የሚተዳደር ቀጣና መፍጠር ነው ብለዋል፡፡

የፒኬኬ ታጣቂዎች ድንበር ተሻግረው ቱርክ ሲገቡ በአሜሪካና አውሮፓ ሕብረት በኩል ‹‹አሸባሪዎች›› ተብለው ይፈረጃሉ፡፡ ነገር ግን በሶሪያ ምድር ተመልሰው ሲመጡ የሶሪያ ዴሞክራቲክ ኃይል የሚዋጋበት ዓላማ አካል በመሆን ለዴሞክራሲ ዋጋ ለመክፈል የሚፋለሙ የሽምቅ ተዋጊዎች ሆነው ይገኛሉ፡፡ በቱርክ ይሁን በሶሪያ ድንበር ፒኬኬ ተመሳሳይ ዘዴ ይጠቀማሉ፣ በተመሳሳይ ግቦች ያምናሉ፣ እንዲሁም በተመሳሳይ ሰብአዊነት የተመሰረቱ ናቸው። ይህም ዋይ ፒ ጂ ማለት ፒኬኬ ነው፡፡

ዕድሜያቸው ለውትድርና ግዳጅ ያልደረሱ ህጻናት በፒኬኬና ዋይ ፒ ጂ ተገደው እንዲታጠቁ ይደረጋል፡፡ ይታገዳሉ እንዲሁም ይገደላሉ፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኩርዶች ሙሉ በሙሉ ከሚባል የድብቅ ተዋጊነት ወደ ግልጽ የግንባር ተፋላሚነት መጥተዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ የአሸባሪዎች ቡድን ለነጻነት የሚታገል አብዮታዊ ንቅናቄ በሚል ስም የፈጸሟቸው አያሌ ግፍ እገታዎችና ግድያ ጨምሮ አሉ።እንዲሁም በአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪነት መሳተፋቸው አልተዘገበም፡፡ የኩርዲሽ ቤተሰቦች ፒኬኬ አናሳዎችን ማገት እንዲያቆም ይፈልጋሉ፡፡

ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ቱርክ 91ኛ የብሔራዊ የህጻናት ቀኗን ማክበሯ ይታወሳል፡፡ በእለቱ በምዕራብ ቱርክ የህጻናት ቀን በማክበር የነበሩ ቱርካውያን ዕድሜያቸው 14 እና 16 የሆኑ 25 የሚሆኑ ነበሩ።እነዚህ ህጻናት ግን በኩርዲስታን የሰራተኞች ፓርቲ / ፒኬኬ ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል፡፡

ፒኬኬ ባለፉት ስድስት ወራት ከ330 በላይ ህጻናትን ያገተ ቢሆንም በአካባቢው ቀድሞ ፓርቲውን ለመቃወም፣ ለመፋለምና ልጆቻቸውን እንዲመልስላቸው በመፈለግ እንቅስቃሴ የጀመሩ የቦከም ማሕበረሰብ ናቸው፡፡ ፒኬኬ ህጻናትን በውትድርና በማስታጠቅ ወንጀል መፈጸሙን ያመነ ሲሆን በፓርቲው የሚገኙ የታጠቁ 25 ወታደሮች ፎቶዎች እንደሚያሳየው ህፃናቱ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት እንደማይበልጥ ታጣቂ ምርኮኞች ምስል ያሳያል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት በውትድርና ላይ ተሰማርተው ግጭቶች በሚገኙበት አካባቢ ይኖራሉ፡፡ እ..1989 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በህጻናት መብት ከለላ አንቀጽ 38 የወጣ አዋጅ መሰረት በየትኛውም አገር የሚገኝ ፓርቲ ዕድሜው 15 ዓመት ያልሞላው ህጻን በጦርነት ያለበት አካባቢ ቀጥታ ግንኙነት እንዳይኖረው ማረጋገጥ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ ይህን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናትና መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እንዲሁም የጸጥታ ምክር ቤት ህጻናትን በግጭቶችና ጦርነት የማስቀረት እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምሯል፡፡

የፒኬኬ የሽብር ድርጅት ተብሎ መፈረጅ

የኩርዲስታን ሰራተኞች ፓርቲ (ፒኬኬ) ዕድሜያቸው ከሰባት እስከ 12 ዓመት የሆኑ ህጻናትንም አልፎ አልፎ ያስታጥቃል፡፡ እ..2010 የዴንማርክ ዕለታዊ ጋዜጣ በርሊንገስኬ ታይደንዴ በዘገባው፤ በፒኬኬ ማሰልጠኛ ማዕከል 3000 የሚደርሱ ወጣት ሚሊሻዎች ሲኖሩ ዕድሜያቸው ስምንትና ዘጠኝ ዓመት መሆኑን ጠቅሶ ነበር፡፡ በተጨማሪ በካምፑ የታሰረውን የፒኬኬ አመራር የኦካላን ህይወት ታሪክና የፈንጅና ጦር መሳሪያ አጠቃቀም ትምህርት እንደሚቀስሙ ተገልጿል፡፡

ይህ የፓርቲው ሴራ በግልጽ ታትሞ ለህዝብ ይፋ ከሆነ በኋላ በሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠንከር ያለ ትችት ደርሶባቸው ነበር፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ቢሆን የፒኬኬ ፓርቲ ህጻናትን ለውትድርና መመልመል ኢ-ሰብአዊ ድርጊት መሆኑን የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል፡፡ ይሁን እንጂ የኩርዲስታን ሰራተኞች ፓርቲ ፒኬኬ ለሚደርሰው ጠንከር ያሉ ትችቶች እጅ ሳይሰጥ ህጻናትን በተለያዩ መንገዶች የማስታጠቅ ተግባሩን ገፍቶበታል፡፡ በተለይም ከአናሳ ማሕበረሰብ በስፋት ወጣቶቹን እያገተ ያስታጥቃቸዋል፡፡

የኩርዲስታን ተከታይ የሆነውን በሶሪያ የኩርዲሽ ኃይል ዋይ..ጂ ህጻናትን የማስታጠቅ እገዳ በመጣስ 59 የሚሆኑ ህጻናትን በወታደርነት የያዘ ሲሆን አብዛኞቹም እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች ነበር፡፡ እ..2014 በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሪፖርት እንደተጠቀሰው፤ ከ15 ዓመት በታች ህጻናት በውትድርና የመቅጠር ተግባር የጦር ወንጀል መሆኑ ቢጠቀስም የትራምፕ አስተዳደር ግን የዋይ ፒ ጂ ቡድን አሸባሪ ድርጅት መሆኑን ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡ ለዚህም የቀጣናው የአሜሪካ አጋር አድርጎ በማየት አስፈላጊውን ድጋፍ ስለሚያደርግላቸው ህጻናትን ወደ ውትድርና የማስገባት ተግባሩ አጠናክሮ ሲቀጥልበት ይታያል፡፡

ዋይ ፒ ጂ በአካባቢው ራሱን አይ ኤስ ኤስ በማለት የሚጠራውን አሸባሪ ቡድን ስለሚዋጋ አሜሪካ እንደጠንካራ አጋሯ ታየዋለች፡፡ ነገር ግን የትራምፕ አስተዳደር ቡድኑ ገለልተኛ ድርጅት አለመሆኑን ግልጽ አድርጓል፡፡ ከፒኬኬ ፓርቲ ጋር የሚገናኝ ሲሆን ከ18 ዓመት በታች በውትድርና የሚቀጥር ድርጅት መሆኑን ጠቅሷል፡፡ በአጠቃላይ ዋይ ፒ ጂ በሶሪያ የሚገኝ የፒኬኬ ክንፍ ሲሆን እንደ ፒኬኬ ሁሉ ህጻናትን ወደ ውትድርና ያስገባል፡፡ ነገር ግን በሶሪያና ቱርክ ከአሜሪካ በሚያገኘው የጦር መሳሪያና የስልጠና ድጋፍ በንጹኃን ላይ ከፍተኛ ወንጀል ፈጽሟል በማለት ግሎባል ሪሰርች የተሰኘ ተቋም ይፋ አድርጓል፡፡

የፒኬኬ ሴት ታጣቂዎች የኩርዲሽ ወታደሮችን መግደላቸውም ሳውዝ ፍሮንት ድረገጽ ዘግቧል፡፡ የፓርቲው ሴት ታጣቂዎች 160 ወታደሮችን መግደላቸውም ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል ፒኬኬ በዓለም ደረጃ እያደገ ያለው አሸባሪ ድርጅት ከመሆኑ በተጨማሪ አደንዛዥ እጽ በማዘዋወርም ስሙ ይነሳል፡፡ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር የአሜሪካ ግምጃ ቤት ዲፓርትመንት ከፍተኛ የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎች ብሎ ከጠቀሳቸው ዝርዝር ውስጥ ሶስት የፒኬኬ ከፍተኛ አመራሮች መኖራቸው ይታወሳል፡፡ ይሄም የፓርቲው የሽብር ተግባር ዋና የፋይናንስ ምንጭ መሆኑ ይገለጻል፡፡

በሌላ በኩል ዘጋርድያን በድረገጹ እንዳስነበበው፤ በኢራቅ የሚኖሩ 92 በመቶ ኩርዳውያን ድምጽ ሰጪዎች የኩርዲስታን መገንጠልና ሉአላዊነት ይደግፋሉ፡፡ በኢራቅ የሚኖሩ ኩርዳውያን የኩርዲስታን መገንጠል መደገፍ በአረብና ኩርዲሽ መካከል ግጭት ወዳለበት ስፍራ ኢራቅ ወታደሮቿን በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይደር አል አባዲ ትእዛዝ መሠረት መላኳን ተከትሎ ነው፡፡

የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተሟጋቾችን ለማራመድ የሚያስችል አሰራር ባለመኖሩ በሀገሪቱ ውስጥ በአለም አቀፋዊው ተሳትፎ ላይ ብቻ ሊሰሩ ከሚችሉት የአፈፃፀም ጥናት ያነሱ ናቸው ይላሉ፡፡ ከሩሲያና እስራኤል በስተቀር ሁሉም በአካባቢው የሚገኙ አገራትና አብዛኞቹ ዓለም አቀፍ አጋሮችና ህዝበ ውሳኔው የሚቃወሙ ጠላቶች በአካባቢው ያለው የደፈረሰ ሁኔታ ይበልጥ ይበጠብጣል በማለት ስጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

አሜሪካና እንግሊዝ የኩርዲስታን ህዝበ ውሳኔ በአጽኖት በመቃወም ተግባሩን ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ሲሉ ገልጸውታል፡፡ የመገንጠል ህዝበ ውሳኔው ለማስተካከልም ኤርቢልና ባግዳድ ለማስማማት ጥሯል፡፡

ኩርዶች በቀጣናው አራተኛ ከፍተኛ የጎሣ ቡድን ሲሆኑ ራሳቸውን የቻሉ አገር ግን አይደሉም፡፡ የኦቶማን ኢምፓየር ከፈረሰ በኋላ የመካከለኛው ምስራቅ መከፋፈል የኩርድ ህዝቦች በኢራቅ፣ ሶሪያ፣ ቱርክና ኢራን እንዲሁም ብዛት ያለው ቁጥር በውጭ አገራት ዲያስፖራ ሆኖው ተበታትነው ይኖራሉ፡፡ የኩርዲስታን አንድ ሀገር መመስረት በአራቱም አገራት በድንበሮቻቸው ለሚፈጠረው ችግር በመስጋት ሲቃወሟቸው መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ዘገባው ከግሎባል ሪሰርችና ዘ ጋርዲያን ድረገጾች የተገኘ ነው፡፡

 

በሪሁ ፍትዊ

Published in ዓለም አቀፍ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።