Items filtered by date: Tuesday, 10 October 2017

ተወዳጁና ተናፋቂው 32 አገራትን በአንድ ታላቅ መድረክ የሚያገናኘው የዓለም ዋንጫ የክንውን ጊዜ ተቃርቧል።ሩሲያም በቀጣዩ ዓመት የሚካሄደውን የ2018 የዓለም ዋንጫ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አስደማሚ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሽር ጉዷን ተያይዛዋለች።

ታላቁን የእግር ኳስ መድረክ ተሳታፊ ለመሆንም በርካታ የዓለማችን አገራት በማጣሪያ ጨዋታዎች ተጠምደዋል።14 አገራት ታላቁን የእግር ኳስ መድረክ ለመታደም ከወዲሁ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። የአምናው አሸናፊ ጀርመንን ምድቧን በበላይነት በማጠናቀቅ የሩሲያ ትኬት ከቆረጡ አገራት ግንባር ቀደም ናት።ይህን ስታደርገም ብዙ አልተቸገረችም።

ከጀርመን በተጓዳኝ የአምስት ጊዜ የዓለም ዋንጫውን መሳም የቻለችው ብራዚል፤የኤዲን ሃዛርዷ የኬቬን ዴብሩና አገሯ ቤልጄም እስካሁን በማጣሪያው ሽንፈትን ያላስተናገደችው እንግሊዝ ፤ስፔን፤ግብፅ፤ ናይጄሪያ ኢራን ጃፓን፤ሜክሲኮ፣፤ኮስታሪካ፤ፖላንድ፤ሳውዲ አረቢያ እንዲሁም ደቡብ ኮሪያ በዓለም ዋንጫ ለመሳታፍ የሚያስችላቸውን ትኬት ቆርጠዋል።አርጀንቲና ሆላንድን የመሳሰሉ የዓለም ዋንጫው ድምቀቶች በአንፃሩ በመድርኩ ለመሳተፍ አጣብቂኝ ውስጥ ይገኛሉ።

በተለይ አርጀንቲና ድምቀት ከሆነችብት መድረክ ለመሳታፍ በመንገዳገድ ላይ ናት።ባሳላፍነው ሳምንት ከ ፔሩ ጋር ያለግብ መለያየትና ነጥብ መጋራቷን ትከትሎም እድል ፊቱን አዙሮባታል።የሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫው አሸናፊዋ ከ 1970 ጀምሮ ከዓለም ዋንጫው መድረክ ሳትሳተፍ ቀርታ አታውቅም።ሩሲያው ምድረክ መገኘቷ ግን አጠራጣሪ ሆኗል።የዓለማችን ኮከብ ተጫዋች የባርሴሎናው ሊዮኔል አንድሬስ ሜሲም በእግር ኳሱ ታላቅ መድረክ እንደማይታይ ከመነገር አልፎ መታመን ጀምሯል።

ከደቡብ አሜሪካ አገራት መካካል ወደ ሩሲያ ማቅናት የሚችሉት አራት አገራት ብቻ ናቸው።እነዚህ አገራትም በየጊዜው በሚካሄድ ማጣሪያ ከአንድ እስከ አራት ሆነው ማጠናቀቃቸው የግድ ነው።አርጀንቲና አንድ ጨዋታ እየቀራት ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

የዲያጎ ማራዶናዋ አገር የመጨረሻ ጨዋታዋን ከኢኳዶር ጋር ታድርጋለች።ይህ ጨዋታ ለአገሪቱ እጅጉን ወሳኝ የሚባል ነው።ማሸነፍ ደግሞ ብቸኛው አማራጭ ይሆናል።ከኒውዝላንድ ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ ለማድረግ ያበቃታል።ይህን ለማድረግ ደግሞ አገሪቱ በተለይ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለችው አንድ ግብ ብቻ መሆኑ ሲታሰብ የሜሲና ፓውሎ ዲባላን አሊያም የማሪኦ ኢካርዲን ምትሃታዊ እግርና የአሰልጣኝ ጆርጄ ሳምፖሌ ድንቅ የታክቲክ ጥበብን ይጠበቃል።

2014 የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚያ አርጀንቱና አሁን 25 ነጥብ አላት።አምስተኛ ደረጃ ላይ ክምትገኘው ከፔሩ ጋር ያላት ልዩነትም አንድ ብቻ ነው።ፔሩ በግብ ክፍያ ትቀድማለች።ሁለተኛ ያለችው ኡራጋይ 28 ነጥብ አላት።ፓራጎይ በአንፃሩ 24 ነጥብ ሲኖራት ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።አርጀንቲና የመጨረሻ ጨዋታዋን አሸነፈች ማለት በቀጥታ ታልፋለች ማለት ነው።ይህ ካልሆነ ግን ሁሉም ነገር ይፈፀማል።በአገሪቱ እግር ኳስ ታሪክ ላይ ጥቁር ጠባሳ ይፈጠራል።

ኢካዶር ያለፉትን አምስት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ተሸንፋለች።ይህ ማለት ጨዋታው ለአርጀንቲና ቀላል ይሆናል አገሪቱን በቀጥታ ወደ ዓለም ዋንጫው ታመራለች ማለት ግን አይደለም።የሊዮኔል ሜሲ አገር ከኢኳዶር ጋር ባለፉት ጊዜያት ካደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ሁለቱን ተሸንፋለች። በአንዱ ደግሞ እኩል ወጥታልች።ከመሬት ጠለል በላይ ክ 2ሺ ዘጠኝ መቶ ከፍታ ላይ በምትገኘው ኢኳዶር የምታደርገው ጨዋታም ለአርጀንቲና ምጥ ነው።ፔሩ አራተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘውን ኮሎምፒያን ታስተናግዳለች። አርጀንቲና ካላሸነፈች ፔሩ አቻ መውጣት ብቻ በቂዋ ነው።

በሶስተኝነት የምትገኘው ቺሊ አስቀድማ የሩሲያ ትኬት ከቆረጠችው ብራዚል ጋር ትገናኛለች።ወደ ሩሲያ ከሚያቀኑት አገራት መካካል አንዷ ለመሆን ከጫፍ የደረሰችው ኡራጋይ የፍላጎቷን ለማሳካት ከቦሊቪያ ጋር የምታድርገውን ቀጣይ ጨዋታ ነጥብ መጋራት ብቻ ይበቃታል።

ብርቱካናማዎች ሆላንዶች ከአርጀንቲና ጋር የሚመሳሰል እጣ ገጥሟታል።የሶስት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮናዎቹ የሩሲያ ጉዞ ቀላል አልሆነም።ወደ ዓለም ዋንጫ የማቅናቷ ነገር ቁርጡ አልታወቀም።በአመዛኙ ግን ከመሄዷ ይልቅ መቅረቷ ያመዝናል።

ብርቱካናማዎቹ ከፈረንሳይና ከሲውዲን ተከትለው ከምድባቸው ሰንጠረዝ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።ወደ ሩሲያ ለማቅናት ዛሬ ከሲውዲን ጋር ወሳኝ ጨዋታ ይጠብቃቸዋል።ምንም እንኳን በእግር ኳስ የሚሆነው ባይታወቅም፤ ጨዋታ ግን የማይሞከረውን እንደሞሞከር ነው እየተባለ ይገኛል። ምክንያቱ ደግሞ ብርቱካናማዎቹ ወደ ዓለም ዋንጫው የሚወስዳቸውን ትኬት ለደርሶ መልስ ጨዋታ ድረሰው ለማረጋገጥ በሲውዲን መረብ ላይ ሰባት ግን ማስቆጠር ይኖርባቸዋል። የዓለም ዋንጫ ተስፋቸው ላይ ነፍስ መዝራት ይችላሉ።

ሶሪያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከሰላም ርቃለች።ብሄራዊ ቡድኑ ምንም አይነት ድጋፍ አያገኝም። ጨዋታዎችን የሚያደረገውም ዘጠኝ ሺ ማይሎችን አቋርጦ በማሌዥያ ነው።ይህም ሆኖ ግን ከአውስትራሊያ ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ ለማካሄድ የሚያበቃ አስደናቂ ታሪክ ሰርተዋል። ሶሪያ የመጀመሪያውን ዙር ጨዋታም በኦማር አልሶማህ የፍጹም ቅጣት ምት ግብ ከአውስትሪያ ጋር አንድ ለአንድ በመለያየት ነጥብ ተጋርታለች። ውጣት ችላለች።የመልሱ ጨዋታ ዛሬ በሲድኒ ይካሄዳል።

ዌልስ አሁንም ድረስ ምድቧን ትመራለች።ሰሜን አየርላንድም ምድቧን አንደኛ አሊያም ሁለተኛ ሆና የማጠናቀቅ የሰፋ እድል አላት።ሶኮትላንድ ደግሞ ሁለተኛ የመሆኗ ነገር የሰፋ ነው።ምንም እንኳን በማጣሪያው ፍልሚያ በጀርመን ሁለት ጊዜ ብትሸነፍም፤ሰሜን አየርላንድ ከምደባ ከተካተቱት አገራት የላቀ ነጥብ አላት።ሶስተኛ ከምትገኘው ቼክ ሪፐብሊክ በተሻለ ሁለተኛ ሆና በማጠናነቅ ወደ ሩሲያ የማቅናት እድሏ የሰፋ ነው።ይህን ማድረግ ከቻለችም ከ 1986 ወዲህ የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋን ማረጋግጥ ትችላለች።

የሪያል ማድሪዱን ኮከብ ካሬዝ ቤልን ጨምሮ የአርሰናሉን አሮን ራምሴን በስብስቧ የያዘችው ከታላቁ እግር ኳስ ሁነት ጋር ያላት ትውውቅ 1958 ላይ የቆመ ነው።ሁለተኛ የዓለም ዋንጫ ተሳትፏቸውን ለማረጋገጥ አሁን ከጫፍ ላይ ናቸው። ዌልሶች ባሳለፈነው አርብ ጆርጂያን ማሸነፍ ችለዋል።ይሁንና ሪፐብሊክ አየርላንድ ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነት በእጅጉ የተቀራረበ ነው።አየርላንድ ባለፈው ማሸነፏን ተከትሎ በመካከላቸው ያለው ልዩነት እንዳይጠብ ምክንያት ሆኗል።

ሁለቱ አገራት ወሳኝ የሚባል ጨዋታ ይጠብቃቸዋል።የካርዲፉ ስታዲየም አሸናፊም ቢያንስ ሁለተኛ ሆኖ የማጠናቀቅ እድል አለው።ከሁሉ ግን ጨዋታው ለዌልሶች የላቀ እድልን ይሰጣል።ምክንያቱ ደግሞ ዌልስ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ማገኛት የፈለገችውን እውን እንድታድርግ በቂ ነው።

ሰርቢያ ባሳለፍነው ዓርብ ባደረገችው ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረባት ግብ ነጥብ ጥላለች።ቀጣይ ጨዋታዋንም ከጆርጂያ ጋር ትጫወታለች።ሰርቢያ ዳግም መሰል እጣ የሚገጥማት ከሆነ ዌልስ ወይንም አየርላንድ ቀጥታ አላፊ ለመሆናቸውን ማረጋገጫ ያገኛሉ። ሰርቢያዎች በታሪካቸው በዓለም ዋንጫው ለሁለተኛ ጊዜ ለመታደም ማሸነፍ ብቸኛ አማራጫቸው ይሆናል።

በመጀመሪያዎቹ አራት ተከታታይ ጨዋታዎች አራት ነጥብ ብቻ ማስመዝገቧን ተከትሎ ብዙዎች ስኮትላንድ ወደ ሩሲያ ለማቅናት እንደማትችል ቃላቸውን ሰጥተዋል።ይሁንና ሶሎቫኒያን በማሸነፍ ከእንግሊዝ ደግሞ አቻ በመውጣት ሉቲኒያና ማልታን በማሸነፍ ከ 1998 ወዲህ የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ተሳትፋቸውን ለማረጋገጥ ከጫፍ ደርሰዋል።የስኮትላንዶች እጣ ፍንታ አሁን በእጃቸው ላይ ነው።ባሳለፍነው ሳምንት ሃሙስ ስሎቫኪያን ማሸነፋቸውን ተከትሎ ምድባቸውን በሁለተኝነት እንዲመሩ ዋስትና ሰጥቷቸዋል።

ያለፈው ዓመት የአውሮፓ ዋንጫ አስደማሚ ተሳታፊዋ አይስላንድ ባለፈው አርብ ቱርክን ማሸነፏን ተከትሎ ምድቧን መምራት ጀምራለች።የዓለማችን ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የምትመራው ፖርቹጋል የደርሶ መልስ ጨዋታ ማግባቷን ማርጋገጥ ችላለች።ዛሬ ምሽት ከምድብ ለ መሪዋ ሲውዘርላንድ ጋር የምታደርግው ጨዋታ ወሳኝ ነው።

በዓለም ዋንጫው የአምስት አገራት ኮታ በተሰጣት አፍሪካም በተለያዩ አምስቱ ምድቦች ተከፍሎ የሚደረገውን የማጣሪያ ጨዋታ በአንደኛነት የሚያጠናቅቁ አገራት በመድረኩ ለመሳታፍ ይቻላቸዋል። ናይጄሪያ ደግሞ ከአፍሪካ አገራት ወደ ሩሲያ ለማቅናት ከቻሉ አገራት ግንባር ቀደም ናት።ባሳለፍነው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ መሳተፍ ያልቻሉት ንስሮቹ በማጣሪያው ባሳዩት ድንቅ ብቃት ለስድስተኛ ጊዜ በዓለም ዋንጫ መሳትፍ የሚያስችላችላቸውን ማረጋገጫ አግኝተዋል።

በሊቨርፑሉ የፊት መስመር ሞሃመድ ሳላህ የምትመራው ሌላኛዋ አፍሪካዊ አገር ግብፅም ናይጄሪያን ተከትላ ሩሲያ እንደምትደርስ ኮንጎ ብራዛቪልን 2 1 በማሸነፍ አረጋግጣለች።የሰባት ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮን መሆን የቻሉት ፈረሰኞቹ እ ኤ አ1990 ወዲህ ከመጀመሪያ ጊዜ ተሳታፊ ሆነዋል።የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ አልሲሲ በአገራቸው ልጆች በመደሰት ለተጫዋቾቹ ስኬት 85 ሺ የአሜሪካን ዶላር ለእያንዳንዳቸው በሽልማት መልክ ችለዋቸዋል።ድንቁ የፈርኦኖቹ ልጅ መሃመድ ሳላህም የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫውን ለማድረግ ና ለሌላ ወሳኝ የቤት ስራ የመድረኩን በይፋ መጀመር ይናፍቃል።

ቱኒዚያ ሞሮኮና ሴኔጋል ደግሞ ወደ ሩሲያ መድረክ ለማቅናት ምድባቸውን በቀዳሚነት በመምራት ላይ ይገኛሉ። በታላቁ መድረክ ለመታደምም ከጫፍ ደረሰዋል።አፍሪካ ዋንጫው ሻምፒዮኗ ካሜሮብ በአንጻሩ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ካሜሩንና በአፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ ደረጃ ያላት አልጄሪያ ወደ ሩሲያ ለማቅናት አልሆነላቸውም።የሩሲያው የዓለም ዋንጫም ለሁለቱ የአፍሪካ እግር ኳስ ጀርባውን ቢሰጥም የበላይ አገራት በሰሜን አፍሪካ አገራት እንደሚደምቅ ተገምቷል።

 

ታምራት ተሰፋዬ

Published in ስፖርት

ጥሩነሽ በ40ኛው ቺካጐ ማራቶን አዲስ ታሪክ ሰርታለች፤

 

ጥሩነሽ ዲባባ ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ ባስቆጠረው የሩጫ ህይወቷ ኦሊምፒክን ጨምሮ በዓለም ቻምፒዮና ብቃትና ውጤታማነ ቷን አስመስክራለች። የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮና የጥምር የወርቅ ሜዳሊያዎች ባለቤት ሆናለች። በሌሎች ውድድሮችም በርካታ ድሎችን በማስመዝገብ የአገሯንም ሆነ የሯሷን ስም ከፍ አድርጋ አስጠርታለች። በተለይ በምትታወቅበት የመም ውድድሮች አስርና አምስት ሺ ሜትር ብቃቷን ጠብቃ በውጤታማነት ዓመታትን በማስ ቆጠር የረጅም ርቀት ንግስት መሆኗን አስመስክ ራለች።

ጥሩነሽ ዲባባ በዓለም ቻምፒዮና ስድስተኛ ሜዳሊያዋን ባለፈው ለንደን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ ካጠለቀች ወዲህም ሙሉ ትኩረቷን ወደ ማራቶን ማዞሯን በማሳወቅ የመም ውድድሮች ዝናና ክብሯ የአርባ ሁለት ኪሎ ሜትር ለመድገም ወስናለች። ለዚህ ፍላጎቷና ውጤኗ ስኬታማነትም ከለንደን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የአስር ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ ክብር መልስ ብርቱ ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች።

ወርልድ ማራቶን ሜጀርስ በመባል ከሚታወቁት ስድስት ታላላቅ የዓለማችን ማራቶን ውድድሮች አንዱ የሆነውና እ..አ ከ1977 የተጀመረውን የቺካጎ ማራቶን ደግሞ የሩጫ ህይወቷን አዲስ ታሪክ ለመፃፍ የቻለችበት የመጀመሪያ ውድድሯ ሆኗል።

ዘወትር የኬንያውያን አትሌቶች የበላይነት የሚጎሉበት የአሜሪካው የቺካጎ ማራቶን ዘንድሮም ከትናንት በስቲያ በደመቀ መልኩ ተካሂዷል። በርካታ ስመ ጥር አትሌቶች የተሳተፉበት ይህ ውድድር ግን ለኢትዮጵያዊቷ ድንቅ ልጅ ድንቅ ውጤትን የለገሰ ሆኗል። ጥሩነሽ ውድድሩን 2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ31 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመጨረስ አሸናፊ መሆን ችላለች። የውድድሩ አሸናፊነትም ስምና ታሪክም ዳግም ወደ ሌላኛዋ ምስራቅ አፍሪካዊት አገር ፊቱን እንዲያዞር ምክንያት ሆናለች።

ውድድር እስካሁን ካደረገቻቸውን ሦስት የተለያዩ የማራቶን ውድድር መድረኮች ወርቅ ያመጣችበት የመጀመሪያው የቺካጎ ድሏም በመድ ረኩ ለአትሌቷ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ውያን አትሌቶች አዲስ የድል ምዕራፍ የከፈተ ሆኗል።

ውድድሩን ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ድረስ ያለማቋረጥ በመምራት ያከናወነችና በአስደናቂ ብቃት ያጠናቀቀችው ጥሩነሽ፤ በአዲስ ምዕራፍ አዲስ ታሪክ ካስመዘገበችበት ውድድር በኋላ እንደገለፀችውም ፤ የቺካጎ ማራቶንን ለማሸ ነፍ ጠንካራ ዝግጅት ማድረጓን የተናገረችው ጥሩነሽ ዲባባ «ለወድድሩ በቂ ዝግጅት አድርጌ አለሁ፤ ብቻዬን እንደመራሁ ነው የጨረስኩት፤ በማሸነፌ በጣም ደስ ብሎኛል፣ ከአሁን ወዲህ ትኩረቴ በማራቶን ውድድሮች ላይ ነው፤ የርቀቱን ክብረ ወሰን መስበር እፈልጋለሁ፤ ለዚህም አስፈላጊውን ዝግጅት አደርጋለሁ» ስትል ገልፃለች።

ኬንያዊቷ ብሪጊድ ኮስጌ በ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ22 ሰከንድ ሁለተኛ ስትሆን፣ አሜሪካዊቷ ጆርዳን ሃሳይ በ35 ሰከንዶች ዘግይታ ሦስተኛ በመሆን ውድድሯን ጨርሳለች። በወንዶቹ ምድብ ደግሞ አሜሪካዊው ጋለን ሩፕ በ2 ሰዓት ከ09 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ በመግባት አሸናፊ ሲሆን፣ ኬንያውያኑ ኪሩይ እና በርናርድ ኪፕየጎ ደግሞ ሁለተኛ እና ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል።

ይህ ውድድር ዓለምአቀፍ ተቀባይነቱ እየጨመረ መጥቶ በየዓመቱ መስከረም መጨረሻ ላይ መካሄድ የጀመረውም እ..አ ከ1983 ጀምሮ ነው። በውድድሩ አርባ ዓመታት ታሪክ ውስጥ በርካታ የዓለማችን ኮከብ አትሌቶች ተፋልመዋል። በውድድሩ የመጀመሪያ ዓመታት አሜሪካውያኑ አትሌቶች የበላይነት ነበራቸው። በርካታ የዓለማችን ጠንካራ አትሌቶች መጀመሪያ ላይ ተወዳዳሪ ካለመሆናቸው ጋር በተያያዘ ሊሆንም ይችላል አሜሪካውያን አትሌቶች በወንዶች ስምንት ጊዜ በሴቶች ደግሞ አሥራ ሁለት ጊዜ አሸናፊ በመሆን በውድድሩ ደማቅ ታሪክ አላቸው። ውድድሩ ተቀባይነቱ እየጎላ የዓለም አትሌቲክስም እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ግን አሜሪካውያን የአሸናፊነት ዘውዱን ለሌሎች አገር አትሌቶች አሳልፈው መስጠታቸው አልቀረም።

በረጅም ርቀት ውድድሮች ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ያህል ጎልተው በመውጣት የባህል ስፖርታቸው እስኪመስል ድረስ የበላይነትን የያዙት ምስራቅ አፍሪካውያን አትሌቶች የአሸናፊነት ዘውዱን ተረካቢ እንደሆኑ መገመት አይከብድም። በዓለም አትሌቲክስ ታሪክ ውስጥ በነዚህ ዓመታት ምስራቅ አፍሪካውያን አትሌቶች በተለይም ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን በቺካጎ ማራቶን ብቻም ሳይሆን በየትኛውም የረጅም ርቀት ውድድር ላይ ፍፁም የበላይነቱን መውሰዳ ቸው በቺካጎ ማራቶንም ተመሳሳይ ታሪክ መፈጠሩ የግድ ነው።

ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶች ማራቶንን ጨምሮ በዓለማችን የተለያዩ የረጅም ርቀት ውድድሮች ላይ ባላንጣዎች እንደመሆና ቸውም ታሪካቸውም ብዙ ልዩነት አይታይበትም። በቺካጎ ማራቶን ግን የሁለቱ አገራት አትሌቶች የአሸናፊነት ታሪክ የጎላ ልዩነት የሚታይበት ብቸኛው ውድድር ነው። ይህ ልዩነት ከወንድ አትሌቶች አኳያ ሲሆን ደግሞ ፍፁም የአንድ አገር የበላይነት የሚንፀባረቅበት ሆኖ እናገኘዋለን።

የቺካጎ ማራቶን የሴት አትሌቶች ታሪክ ላይ ኬንያውያን ከኢትዮጵያውያን አኳያ የበላይነት ቢኖራቸውም ልዩነቱ እንደ ወንዶቹ የተጋነነ አይደለም። ኢትዮጵያዊቷ ብርሃኔ አደሬ እ..2006 ይህን ውድድር አሸንፋለች። ብርሃኔ በቀጣዩ ዓመትም የዚህ ድል ባለቤት ከመሆኗ ባሻገር እስካለፈው ዓመት ውድድር ድረስ በተከታ ታይ የቺካጎ ማራቶን ሁለት ጊዜ ያሸነፈች ብቸኛዋ የዓለማችን አትሌት በመሆን እስካለፍ ዓመት ድረስ ቆይታለች። ባለፈው ዓመት ውድድር በኬን ያዊቷ ፍሎሬንስ ኪፕላጋት 2:21:32 በሆነ ሰዓት ማሸነፏን ተከትሎ የብርሃኔን ታሪክ መጋራት ችላለች።

ይህን ውድድር ማሸነፍ የቻለች ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አፀደ ባይሳ ነች።አፀደ እ. . 2010 ይህን ድል ማሸነፍ የቻለች ሲሆን፣ የገባችበት ሰዓትም፤ 2:23:40 ሆኖ የተመዘገበ ነው። 2011 እጅጋየሁ ዲባባ 2:22:09 በሆነ ሰዓት አሸናፊ ስትሆን፣ አፀደ ባይሳ ዳግም 2:22:03 በሆነ ሰዓት 2012 ላይ ወደ ድል ተመልሳለች።

2013 ውድድር ዓመት ኬንያውያን በሪታ ጂፕቶ አማካኝነት ከአስራ አንድ ዓመት በኋላ ወደ ድል የተመለሱበት ነው።ይሁን እንጂ ጂፕቶ አበረታች መድኃኒት ተጠቃሚ ሆና በመገኘቷ ውጤቷ ተሰርዞ ሁለተኛ ሆና ላጠናቀቀ ችው ኢትዮጵያዊት አትሌት ማሬ ዲባባ ከወራት በፊት መመለሱ ይታወሳል።

ቀጣዩ ዓመትም የዓለም ቻምፒዮኗ ማሬ ዲባባ 2:25:37 በሆነ ሰዓት ኢትዮጵያውያን ከቺካጎ ማራቶን ድል እንዳልራቁ ያሳየችበት ነበር።ከማሬ ዲባባ በኋላ ያለፉት ሁለት ውድድሮች የፍሎሬንስ ኪፕላጋት ወርቃማ ዘመናት ሆነዋል።

አሜሪካውያን ሴት አትሌቶች አስራ ሁለት ጊዜ በቺካጎ ማራቶን ሲያሸንፉ ኬንያውያን ሰባት ጊዜ፤ ኢትዮጵያውያን ስድስት ጊዜ በማሸነፍ በውድድሩ ደማቅ ታሪክ አላቸው።እንደ አጠቃላይ ግን ኬንያውያን በሁለቱም ፆታ ሃያ ሦስት ጊዜ በማሸነፍ አውራውን ስፍራ ይይዛሉ።አሜሪካውያን ሃያ ጊዜ በማሸነፍ ሲከተሉ እንግሊዛውያን ስምንት ድሎችን፤ ኢትዮጵያውያን ሰባት ድሎችን በማጣጣም ስማቸው በውድድሩ የታሪክ ማህደር ሰፍሯል።

የቺካጎ ማራቶን ክብረወሰን ከአሥራ አምስት ዓመት በፊት እ..2002 ላይ የዓለምን የማራቶን ክብረወሰን እስካሁን ባላስደፈረችው እንግሊዛዊት አትሌት ፓውላ ራድክሊፍ የተያዘ ነው። ሰዓቱም 2:17:18 ሆኖ በውድድሩ ማህደር ሰፍሯል።የሰላሳ አንድ ዓመቷ ጥሩነሽ ሙሉ ትኩረቷን ባላደረገችበትና ብዙም ልምድ ባላካበተችበት የለንደን ማራቶን ባለፈው ሚያዚያ ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ 2:17:56 የሆነ ሰዓት ማስመዝገቧም ይታወሳል።

 

ታምራት ተስፋዬ

 

 

Published in ስፖርት

ዛሬ ዛሬ በከተማችን ዘመናዊ ስልጣኔ ጣራ በነካበት ዘመን የሴትን ልብ ለመማረክ ወንዶቻችን በርካታ ተግባራትን ሲፈፅሙ ይስተዋላል፡፡ ወንዱ ለሴቲቱ ያለውን ፍቅር ለመግለፅ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች መካከልም አማላይና ተወዳጅ ቃላቶችን ማዥጎድጎድ ይገኝበታል፡፡

በሌላ በኩልም በተለይም በከተሞች አካባቢ ከአበባ ጀምሮ እንደ መኪና ፣ገንዘብና ቤት የመሳሰሉ ነገሮችን በማቅረብ ልብን ለማሸፈት እንዲሁም የወደዷትን የራስ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት አለ፡፡

በሀገራችን ባህል በተለይም በገጠሩ አካባቢ ደግሞ ሁኔታው ሌላ ገጽታ ነው የሚኖረው ምክንያቱም መተጫጨቱም ሆነ አስፈላጊው ነገር በሙሉ የሚያልቀው በቤተሰብ በኩል በመሆኑ ነው።

ወንዶች ሴቶችን ለጋብቻ ለማጨት በርካታ ነገሮችን ቢያደርጉም የሄኛው ግን ፍፁም ከከተማውም ይሁን ከገጠሩ የተለየ ነው፡፡፡ ለአብነት እንኳን በደቡብ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በሱርማ ባህል አንድ አፍላ ኮበሌ ቀልቡ የወደዳትን ልጃገረድ ለጋብቻ ለማጨት ከአቻው ጋር በረጃጅም ጠንካራ ልምጭ ይገረፋል፡፡ እድል ከቀናው ተቀናቃኙን ረቶ የተመኛትን ኮረዳ በእጁ ያስገባል፤ ካልሆነለትም ደሙን እያዘራ ለሚቀጥለው ፍልሚያ ራሱን ያዘጋጃል፡፡ በሐመር ደግሞ አንድ ወጣት አንዲትን ኮረዳ ማግባት የሚችልው ምን አልባትም ከአስር በላይ በተደረደሩ በሬዎች ጀርባ ላይ ተረማምዶ ሮጦ ማለፍ ከቻለ ብቻ ነው፡፡ የአንዱ ባህል ከሌላኛው የተሻለ ነው ማለት ባይቻልም ጉዳት ከመቀነስ አንፃር ግን የሐመሮቹ በጥቂቱም ቢሆን ሳይሻል አይቀርም ፡፡

ቢ ቢ ሲ ከሰሞኑ ከአፍሪካችን የደሴት ሀገር ማዳጋስካር ይዞት ብቅ ያለው ዘገባ የሴትን ልብ ለማሸነፍና ጋብቻ ለመፈፀም እንዲህም ይደረጋል እንዴ? ያስባለ ነው፡፡ ዘገባው እንደሚያሳየው ከሆነ በማዳጋስካር በየዓመቱ የሚካሄድ አንድ ትልቅ ባህላዊ ውድድር አለ፡፡ ይህውም «የቤስቲሊዮ» መንደር ወንዶች የሴቶችን ቀልብ ለመሳብና ለጋብቻ ለማጨት ከጠገቡ በሬዎች ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ፍልሚያ ወንዶቹ በእጃቸው የሚይዙት አንዳችም ነገር አይኖርም፡፡ በቃ ባዶ እጃቸውን የበሬው ሻኛው ላይ በመንጠልጠል በሬውን አድክሞ ታግሎ መጣል ነው፡፡ ለውድድሩ የሚቀርቡት በሬዎችም እንደ ገዳይ ሳይሆን ቅዱስ ተደርገው ይቆጣራሉ፡፡ በዚህ ከበሬዎች ጋር በሚደረግ የፍልሚያ ውድድር ላይ ታዲያ ለልጃገረዶች ጥሩ የመዝናኛ አማራጭና እርስ በርስ የመገናኛ መድረክ ሲሆን ለተፋላሚ ወንዶች ደግሞ ለጋብቻ የሚሏትን ልጃገረድ ማግኛ ሁነኛ አማራጭ ነው፡፡

በውድድሩ በአብዛኛው ወንዶች ሴቶችን ለመማረክ ከበሬዎች ጋር በሚያደርጉት ፍልሚያ ከከባድ ጉዳት እስከ ሞት ድረስ ሊደርስባቸው ይችላል፡፡ ባጭሩ የወደዷትን ለማግኘት የህይወት መስዋዕትነት ይከፍላሉ፡፡ ውድድሩን አድርገው ተሸናፊ የሆኑ ወጣት ወንዶች የጋብቻ ጊዜያቸው ካለፈና ልጆች ካልወለዱ በማህበረሰቡ ስለሚወገዙና ከጎሳ አባልነታቸው ስማቸው ስለሚፋቅ በየዓመቱ ውድድሩን እስኪቀናቸው ድረስ ያካሂዳሉ፡፡

የሚገርመው ነገር አንድ ወጣት ከበሬ ጋር ተፋልሞ በውድድሩ መሰረት በሬውን አድክሞ ማሸነፉን ካረጋገጠ በኋላ ወደሚፈልጋት ሴት ሄዶ ለጋብቻ ቢጠይቃት ምን አልባት ከበሬው ጋር ሲፋለም ያሳየው ጥበብ ካልማረካት ‹‹አይ በሚቀጥለው ዓመት ሞክር ተወኝ›› ማለት መቻሏ ነው፡፡ ታዲያ ወንዱም በአሁኑ እንዳልተሳካለት ተረድቶ በቀጣይ ለእርሱ የምትሆነውን ልጃገረድ ለማጨት አሁንም ከበሬ ጋር ትግሉን ይቀጥላል፡፡

በዚህ በምስራቃዊ ማዳካስካር በቤስቲሊዮ መንደር በሚካሄደው ሳቫኪያ በተሰኘው ወጣት ወንዶች ሴቶችን ለጋብቻ ለማጨት ከበሬዎች ጋር በሚያደርጉት ትግል ቢያንስ እስካሁን 50 ወንዶች ህይወታቸውን እንዳጡም ነው የቢቢሲ ዘገባ የሚያስረዳው፡፡

 

አስናቀ ፀጋዬ

 

 

Published in መዝናኛ

አሁን አሁን ዘመን አመጣሽ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አብዝቶ መጠቀም የስልጡን ሰው መገለጫ እየሆነ መጥቷል፡፡ በተለይም ተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይ ያሉ ጨዋታዎችን መጫወት፣ ላፕ ቶፕ ኮምፒውተሮችን ከፍቶ መቀመጥ እንዲሁም ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠ ቀም ሱስ የሆነባቸው በርካ ቶች ናቸው። የቴክኖሎጂ ውጤቶቹን በአግባቡና እንደአስ ፈላጊነቱ መጠቀም ወሳኝ መሆኑ ቢታወ ቅም ቅጥ ያጣ ከሆነና የበዛ የሆነ እንዲሁ የራሱን ጉዳት ይዞ መም ጣቱ አይቀርም።

በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ባህልና ወግ ወደማይፈለግ አቅጣጫ እንዲያመራ በማድረጉ በኩል ሚናው ላቅ እያለ የመጣም ይመስላል። ልጆች ከቤተሰቦቻ ቸው አልያም ከእሀት ወንድሞቻቸው ጋር እንዳይጨዋወቱ ቤተሰባዊ ግንኙነቶችም እጅጉን የላሉ እንዲሆኑ በማድረግም በኩል እነዚህ ዘመን አመጣሽ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተፅእኖ እያሳደሩ ይገኛሉ።

ከሁሉም በላይ የሚያሳስበው ጉዳይ ደግሞ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን አልያም ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ለልጆቻችን የምናስተላልፍበት መንገድ ነው። በእድሜያቸው ማድረግ የሚገባቸውን እንዳያደርጉ ብሎም በጨዋታና በሌሎች በሚመጥኗቸው ነገሮች ወስጥ አልፈው የልጅነት ትዝታ እንዳይኖራቸው በማድረግ በኩልም እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እየፈጠሩ ያሉት ችግር እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

አሁን አሁን ትምህርት ቤቶችም በሁኔታው እጅግ በመጨነቃቸው ምክንያት ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ሲገቡ የቴክኖሎጂ ውጤቶቹን ይዘው እንዳይመጡ ህግ ከማውጣት ጀምሮ ሲገቡ እስከመፈተሽ የሚደርስ እርምጃን እየወሰዱም ነው።

አሁን አሁን ግን ከምንም በላይ እያሳሰበ የሚገኘው ጉዳይ እነዚህን የቴክኖሎጂ ውጤቶች አብዝቶ በመጠቀም የሚከሰተው የጤና ችግር ነው። በተለይም በዓይን ላይ የሚያስከትለው ጉዳት፤ ለዚህ ደግሞ ማሳያ የሚሆነን ኦዲቲ ሴንትራል ከወደ ቻይና ያስነበበን ተመሳሳይ ዜና ነው።

21 ዓመቷ ቻይናዊት ወጣት በአንድ ድርጅት ወስጥ የፋይናንስ ሠራተኛ ናት፤ እናም በሥራዋ ፀባይ ምክንያት ብዙውን ጊዜዋን የምታጠፋው ኮምፒውተርን በመጠቀም ነው ። ይህ መሆኑ ባልከፋ ምክንያቱም የሥራ ጉዳይ ስለሆነ ፤ ወጣቷ ግን ወደ ቤቷ ሰትመለስ ዓይኗን እንዲሁም አእምሮዋን ለማሳረፍ ፍቃደኛ የሆነች አትመስልም። በዚህም እቤቷ ስትገባ እንዲሁም በእረፍት ጊዜዋን የምታሳል ፈው ተንቀሳቃሽ ስልኳን በመጠቀም «ኪንግ ኦቭ ግሎሪ » የተሰኘውን ጨዋታ ያለማቋረጥ በመጫወት ነው። ምንም እንኳን ውጤቱ መልካም ባይሆንም።

ወጣቷ ቀን ከሌት በተጫወተችው በዚህ ጨዋታ እንዲሁም ከሥራዋ ፀባይ አንፃር በዓይኗ ላይ በፈጠረችው ጫና ምክንያት የግራ ዓይኗን ለማጣት ተገዳለች ይላል ዘገባው።

የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ እንደሚ ያመለክተው ወጣቷ እንደ ወትሮው ሁሉ ከሥራ ወደ ቤቷ ገብታ ምግብ እንኳን ሳትመገብ ለሰባት አልያም ለስምንት ሰዓታት ያለማቋ ረጥ በተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ያለውን ጨዋታ ስትጫወት ቆይታ ድካም ሲጫጫናት ነው ወደ መኝ ታዋ ያመራ ችው ፤ ሆኖም ጠዋት ስትነሳ የግራ ዓይኗ ማየት ተስኖት ነበር።

ይህን የተመለከቱት ቤተሰቦቿ በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል ቢወስዷትም ዓይኗ በተፈጠረበት ከፍተኛ ብርሃንና ባጣው እረፍት ምክንያት ጉዳት አጋጥሞት ወይም ጠፍቶ ነው ያገኙት ፤ ይህ ሁኔታ በአብዛኛው እድሜያቸው በገፉ ሰዎች ላይ የሚከሰት ነው የሚሉት የህክምና ባለሙያዎቹ የእርሷ ጉዳት ከእድሜዋ አንፃርም እጅግ ከፍተኛና አስቸጋሪ ምናልባትም ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ የማይቻል እንደሚሆን በመናገር ላይ ናቸው ።

ወጣቷ ችግሩ ካጋጠማት ከአንድ ሳምንት በላይ ቢሆናትም እስከ አሁን ሆስፒታል ውስጥ የህክምና እርዳታ እየተደረገላት ይገኛል፤ በውጤቱም የተወሰነ የብርሃን ጭላንጭል ቢታያትም የቀድሞ እይታዋን ግን መመለስ አልቻለችም ይለናል ዘገባው፡፡

ጉዳዩ በአገሪቱ ያሉ የመገናኛ ብዙኅንን ቀልብ የሳበ ከመሆኑም በላይ የተንቀሳቃሽ ስልክ ጨዋታው ሱስ ያለባችሁ እንዲሁም ሥራችሁ ከመሰል የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር የሆነ የህብረተ ሰብ ክፍሎች በተለይም ወጣቶች ጥንቃቄ አድርጉ የሚል መልዕክታቸውንም እያስተላለፉ ነው።

ይህ መሰሉ ችግር በእኛም አገር እየሆነ ነውና « ሳይቃጠል በቅጠል» እንዲሉ ሁሉም ነገር በልኩ ሲሆን ጥሩ በመሆኑ ጥንቃቄ ይደረግ እንላለን።

 

እፀገነት አክሊሉ

 

 

Published in መዝናኛ

የኢትዮጵያ ድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ሥርዓት ገና ያልዳበረ እና ሰፊ ሥራን የሚጠይቅ እንደሆነ የሕክምና መስኩ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በአገራችን በድንገተኛ ሕክምና ልዩ መስክ ወይም ስፔሻሊቲ የሰለጠኑ ሐኪሞች ሃያ አንድ ብቻ መሆናቸው የኢትዮጵያ ድንገተኛ ሕክምና ባለሙያዎች ማህበር መረጃ ያስረዳል። ይህም አገልግሎቱ ገና በማደግ ላይ ያለ መሆኑን አመላካች ነው። የኢትዮጵያ ድንገተኛ ሕክምና ባለሙያዎች ማህበር መስራቾች አንዱና በፕሬዚዳንትነት እየሰሩ ያሉት ዶክተር አክሊሉ አዛዥ በሕክምናው ምንነት፣ በዕድገቱና መሻሻል ስለሚገባቸው ጉዳዮች ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ያደረጉትን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

አዲስ ዘመን ፡- ድንገተኛ የሕክምና አገልግሎት ምን ማለት ነው?

ዶክተር አክሊሉ፡- ድንገተኛ ሕክምና በሆስፒታሎችና በጤና ጣቢያዎች አስቸኳይ ሕመም ወይም አደጋ ለደረሰባቸው ሰዎች የሚሰጥ የነፍስ አድን ሕክምና ሲሆን፣ ይህም የሰው ህይወትን በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ከማለፍ መታደግና ተጎጂ ዘለቄታዊ ሕክምና የሚያገኝበትን ዕድል የማመቻቸት አገልግሎት ነው። የሕክምና አገልግሎቱም ታካሚው ከቤቱ ወይም አደጋ ከተከሰበት ቦታ ጀምሮ የሕክምና ተቋም እስኪደርስ የመጀመሪያ የሕክምና እርዳታ የሚያገኝበት ከመሆንም አልፎ ከመደበኛ ሕክምና ሰጪ ባለሙያዎች ጋር በተግባቦት ሥርዓት በመደጋገፍ የታካሚውን ህይወት ለማቆየት የሚደረግ ጥረትም ነው። ይህም በቅድመ ሆስፒታል ወይም በአንቡላንስ ቡድን ድጋፍ ይከናወናል። ሕብረተሰቡ ጭምር ይሳተፍበታል።

አዲስ ዘመን፡- የአገራችን የአደጋ ተጋላጭነት ደረጃ ምን ይመስላል ?

ዶክተር አክሊሉ፡- የትኛውም አገር ከአደጋ ተጋላጭነት ነፃ አይደለም። በአገራችን የትራፊክ አደጋ በርካታ ሞትና አካል ጉዳት እያስከተለ ከጊዜ ወደ ጊዜም የአደጋው መጠን እየጨመረ ይገኛል። በሌላ በኩል የኮንስትራክሽን ዘርፉ መስፋፋት የሰራተኞች የመውደቅ አደጋ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም በአገራችን የተሽከርካዎች መብዛት፣ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ የግንባታና ኢንቨስትመንት ማደግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ካልተደረገ ድንገተኛ አደጋዎች እየጨመሩ ይሄዳሉ። ሌላው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በዓለም ላይ እንደ ኢቦላ፣ ሳርስንና መርስን የመሳሰሉ ፈታኝ የበሽታ ወረርሽኝና ተላላፊ በሽታዎች ሊፈጠሩ ችለዋል። ሌሎች ከፍተኛ ድንገተኛ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ እንደ የሽብር ጥቃት የመሳሰሉት ችግሮችም አሉ። ከነዚህ ሁሉ እኛ ነፃ ነን ማለት አንችልም፤ ስለሆነም ዝግጁነት ያስፈልጋል። ለተጠቀሱት ጅምላ ድንገተኛና መደበኛ ድንገተኛ አደጋዎች ሁሉ በተገቢ አኳኋን ዝግጁ ሆነን መጠበቅ አለብን።

አዲስ ዘመን፡- በአገራችን የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት በየትኞቹ የህክምና ተቋማት ይሰጣል?

ዶክተር አክሊሉ፡- የሕክምና አገልግሎቱ በሁሉም ሆስፒታሎች ይሰጣል። ነገር ግን በልዩና ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ የአለርት የአደጋ ማእከል እንዲሁም በጎንደር፣ ሃዋሳ፣ አዳማና ዓይደር መቀሌ ሆስፒታሎች ልዩ የድንገተኛ ሕክምና ማእከላት ተቋቁመዋል።

አዲስ ዘመን፡- የአገራችን የድንገተኛ ሕክምና ዘመናዊነትና ተደራሽነት እንዴት ይመለከቱታል?

ዶክተር አክሊሉ፡- አሁን ጥሩ ጅማሮ ላይ እንገኛለን። በአፍሪካም ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ኢትዮጵያ በሁለተኝነት ትቀመጣለች። ከሌሎች የአፍሪካ አገራት በላይ አሁን ላይ ለድንገተኛ ሕክምና የትምህርት መስክ ላቅ ያለ ትኩረት ሰጥታለች። የአምቡላንስ አገልግሎቱ እያደገ ነው። ከአስር ዓመት በፊት በወረዳዎች የነበረው የአንቡላንስ ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። አሁን በመላ አገሪቱ 1600 አምቡላንሶች አሉ። ይህ ማለት በእያንዳንዱ ወረዳ አንድ ወይም ሁለት አምቡላንስ አለ። ነገር ግን በነዚህ አምቡላንሶች በድንገተኛ ሕክምና የሰለጠነ ባለሙያ አለ ማለት ግን አይደለም። በቂ ባለሙያዎች ማፍራት ይጠበቅብናል። የአደጋ ማዕከላትንም እያቋቋምን ነው። ነገር ግን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ያላቸው ቅንጅት ግን ብዙ የሚቀረው ነው። በዚህም የብዙ ዜጎች ህይወት ያልፋል። እኛም ይሄን ክፍተት ለይተን በመስራት ላይ ነን። አገልግሎቱ የተዋጣለት አስተዳደር እንዲሁም የቁጥጥርና ግምገማ ያስፈልገዋል። የግብዓት እጥረት በየጊዜው ማሟላት ያስፈልጋል። የሰው ኃይልም በበቂ መጠን ለማፍራት ማህበሩ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ጥረት እያደረግን እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፡- የአገራችን የድንገተኛ ሕክምና ሥርዓት ክፍተቶችን ቢጠቅሱልኝ?

ዶክተር አክሊሉ፡- የአገልግሎቱ ሥርዓት አለመጠናከር ትልቁ ክፍተት ነው። ኀብረተሰቡ የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ እንዲሁም አምቡላንስ ማግኘት የሚችልበት የተግባቦት መስመር ወይም አርተሪ በበቂ መጠን መዘርጋት አለበት። ይህን የትብብርና የግንኙነት አሰራር ማጠናከር ያስፈልጋል። የግብዓት እጥረትና በሆስፒታሎች ለድንገተኛ ሕክምና ክፍል የሚመደበው ቦታ በጣም ትንሽ መሆኑ ሌላው ችግር ሲሆን የጤና ተቋማትም ዝግጁነት ይጎድላቸዋል። ይህም ራሱን የቻለ ማነቆ ነው። የኀብረተሰቡ የግንዛቤ ማነስ መቀረፍ ያለበት ጉዳይ ነው። የመጀመሪያ እርዳታ ግንዛቤ ማሳደግ ኀብረተሰቡ ራሱ ቀድሞ እንዲከላከል ያስችለዋል። ይህም የድንገተኛ ሕመሞችን ምንጭን የምናደርቅበት ሁኔታ ይፈጥራል። አደጋ በሚደርስበት ወቅትም ማስቀረት የሚቻሉ ሞቶችን ይቀንሳል። በድንገተኛ አደጋ ምክንያት ከሚከሰቱ ሞቶች የሚበዙት በመጀመሪያው ሰዓት የሚከሰቱ በመሆናቸው ግንዛቤ ያለው ሰው የአየር ትቦ እንዲከፈት በማድረግ፣ የደም መፍሰስን ማስቆም፣ አተነፋፈስን ለማስተካከል መርዳት፣ ጉዳቱን የሚያባብሱ አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን መከላከል ይቻላል። በዚህም የሚደርሱ ሞቶችን እና የአካል ጉዳቶችን መቀነስ ያስፈልጋል። የጤናን ጉዳይ በትምህርት ውስጥ አካቶ ልጆችን እያስገነዘብን ስንሄድ ችግሩ ይቀረፋል። ዘለቄታዊ መፍትሔም ማምጣት ይቻላል። አሁን ችግሩን ለመቀነስ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ለ1 መቶ ሺ የኀብረተሰብ ክፍሎች አጫጭር ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ይሰጣል። ስልጠናው እውቀትና ክህሎትን የሚያስጨብጥ በመሆኑ በድንገተኛ አደጋ ወቅት ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ ከማን ጋር መገናኘት እንደሚጠበቅና አደጋና ሕመሞችን ለመለየት ይረዳል። ይህም አገልግሎቱን ያቀላጥፈዋል።

አዲስ ዘመን፡- በአገራችን የድንገተኛ ሕክምና ትምህርትና ስልጠና ምን ይመስላል?

ዶክተር አክሊሉ፡- በአዲስ አበባ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስር በጠቅላላ ሕክምና የተመረቁ ሐኪሞች በስፔሻሊቲ ደረጃ ሦስት ዓመት የሚሰለጥኑበት መርሐ -ግብር አለ። ሌላ በድህረ-ምረቃ የድንገተኛና ፅኑ ሕሙማን ሕክምና የሁለተኛ ዲግሪ እያሰለጠነ ይገኛል። አሁን በቅርቡ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሐ-ግብር በአስር የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎችና ከፍተኛ ሆስፒታሎች መሰጠት ጀምሯል። በዩኒቨርሲቲው አንድ የድንገተኛ ሕክምና ማሰልጠኛ ማእከል ይገኛል። በዚህ የስልጠና ማእከል አንድ ሺ ሁለት መቶ ሐኪሞች የሰባት ሳምንት የድንገተኛ ሕክምና ስልጠና ወስደዋል። የሕክምና መስኩ የስፔሻሊቲ ትምህርት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልም እየተሰጠ ይገኛል።

አዲስ ዘመን፡- ማህበሩ የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎትን ለማስፋፋትና ለማዘመን ያበረከተው አስተዋፅኦ ምን ይመስላል?

ዶክተር አክሊሉ፡- እንደ ማህበር ወሳኝ አቅጣጫዎች አሉን። በመጀመሪያ ደረጃ የአባል ሐኪሞች ብቃት ማሳደግና ወቅቱን የጠበቀ ክህሎት እንዲይዙ ማድረግ ነው። ይህም ለተገልጋዮች የምንሰጠው አገልግሎት ጥራት ያለው እንዲሆን ይረዳል። በሌላ በኩል የድንገኛ ሕክምና ለማስፋፋት ማህበሩ ከፖሊሲ አውጪዎች ጋር ተቀራርቦ ይሰራል። ማህበራችን በጤና ጥበቃ ስር የተቋቋመው የድንገተኛና ፅኑ ሕሙማን ግብረ- ሐይል መስራችና ግንባር ቀደም ተሳታፊም ነው። የድንገተኛ ሕክምና የአራት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ሲቀረፅ የበኩላችንን አበርክተናል። ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመተባበር በሐኪሞች አቅም ግንባታ የበኩላችንን በመወጣት ላይ እንገኛለን። ማህበራችን ከተለያዩ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተመሳሳይ የሙያ ማህበራት ዝምድናና ቁርኝት ፈጥረናል። የአፍሪካና የዓለም አቀፉ የድንገተኛ ሕክምና ፌዴሬሽኖች አባል ነን። ይህም ወቅታዊ የሕክምና መስኩ ሳይንስና እውቀት ወደ አገራችን ለማምጣት ተቆራኝተን እንሰራለን።

 

በሪሁ ብርሃነ

 

 

Published in ማህበራዊ

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ትኩረት አድርጎ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች የሚገኙ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮችን በመንደር በማሰባሰብ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡ እነዚህ ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች የሚባሉት አፋር፣ ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሶማሌ ሲሆኑ፣ እንዲሁም በኦሮሚያና በደቡብ ክልል የሚገኙ አርብቶ አደሮችም ይካተታሉ፡፡

እነዚህ ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮች አኗኗራቸውና አሰፋፈራቸው በተበታተነ ሁኔታ ስለሆነ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ተጠቃሚ አልነበሩም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሀገሪቱ በተለያየ ጊዜ የሚከሰተው የሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ አደጋ በቀላሉ የሚጎዱ ሲሆን፣ ድህነትም በከፋ ደረጃ የሚያጠቃቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡

እነዚህን በተበታተነ መልኩ ሰፍረው የሚገኙ ህዝቦችን ለማሰባሰብ መንግሥት የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ የተንቀሳቀሰው ውሃን ማዕከል ያደረገ የመንደር ማሰባሰብ መርሐ ግብር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለአርብቶ አደሩም ሆነ ለከፊል አርብቶ አደሩ ህልውና ዋናው ውሃ ነው። ውሃ ለእነርሱም ሆነ ለሚያረባቸው እንስሳት መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ እሱን ፍለጋ ከቦታ ቦታ መንከራተ ታቸው እሙን ነው። ይሁንና ይህን ድካማቸውን ሊያስቀር የሚችል በጥናት ላይ የተመሰረተ የመንደር ማሰባሰብ መርሐ ግብር በህዝቡ መልካም ፈቃድ በእነዚህ ክልሎች ላይ ይከናወናል፡፡

የመንደር ማሰባሰቡ መርሐ ግብር በጥናት ላይ የመመስረቱ ምስጢር ሰዎች ያለበቂ ምክንያት ከቦታ ቦታ መዘዋወር ስለሌለባቸው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ያሉበት አካባቢ ላይ ቢቆዩ ምን ያገኛሉ ምንስ ያጣሉ እንዲሁም ወደ ሌላ ቦታ ሄደው መስፈራቸውስ በአገርም አሊያም በክልል በዋናነት ደግሞ በራሳቸው ላይ ምን ለውጥን ያመጣል የሚለው ለይቶ ለማከናወን ስለሚያስችል ነው። ይህ ከሆነ በኋላም በአካባቢው ያስፈልጋሉ የሚባሉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲሟሉ ተቋማትም እንዲፈጠሩ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ይሆናል፡፡

ከምንም በላይ ደግሞ በአካባቢው ላይ አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶች በሙሉ በአፋጣኝ እንዲሟሉ ያስችላል፡፡ በእነዚህ ሥራዎች አማካይነትም የዜጎቹ የምግብ ዋስትና የሚረጋገጥበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፤ በተጨማሪም በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችንም በማምረት ከራሳቸው አልፈው የሀገርን ኢኮኖሚ ሊገነባ ወደሚችል እንቅስቃሴም ሊያስገባ ይችላል።

በሌላ በኩልም በመንደር የተሰባሰቡ ሰዎች ሰላማቸው ይጠበቃል፡፡ በተበታተኑ ጊዜ ፀረ-ሰላም ኃይሎች በቀላሉ ሊያጠቋቸው የሚችሉ ሲሆን፣ በአንድ ላይ መሰባሰባቸው ግን በመልካም አስተዳደሩም ሆነ በፀጥታው በኩል የተሻለ ህይወት እንዲመሩ ያስችላቸዋል።

መሰባሰብ ኃይል እንደመሆኑ መጠን በአንድ አካባቢ መገኘታቸውም መብታቸውን ከሌላው በተሻለ ሁኔታ እንዲጠቀሙ ያስችላቸዋል። በተጨማሪም የትምህርት፣ የጤና የኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ የመብ ራት፣ የውሃ፣ የእህል ወፍጮና ሌሎች አስፈ ላጊ ማህበራዊ ተጠሜታዎች እንዲያገኙ ያግዛ ቸዋል፡፡ይህም ጤናማ እና የተረጋጋ ህይወት እንዲመሩ ያስችላቸዋል።

ምርታቸውንም በቀላሉ ለገበያ የሚያቀርቡ በት ዕድል ስለሚያገኙ የተሻለ ኑሮን ለመኖር ይችላሉ፡፡ እንዲሁም ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት መስፋፋት ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር በአንድ አካባቢ መሰባሰባቸው ከግብርና ውጪ ባሉ የሥራ ዘርፎችም ላይ ተሰማርተው ሀብት እንዲያፈሩ መንገድ ይከፍታል፡፡

በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የከፊል አርሶ አደር ተመጣጣኝ ልማት ማረጋገጥ ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ወንድማገኝ ኃይሉ እንደሚሉትም፤ በየዓመቱ በተለይም ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች ላይ መሰራት ያለባቸውን ተግባራት ከክልሎቹ ጋር በመሆን ያቅዳሉ። ከዚህ መካከል አንዱ የመንደር ማሰባሰብ መርሐ ግብር ነው። ይህ ሥራም ከድጋፍ ቦርዱ ጋር በቅንጅት የሚሰራ ሲሆን፣ ክልሎቹ ካሉባቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲላቀቁ በማድረግ በኩል ሰፊ ሚና ተጫውቷል።

ከዚህ አኳያ ከ2003 በጀት ዓመት ጀምሮ የመንደር ማሰባሰብ ሥራው በተቀናጀ መልኩ በመከናወን ላይ ይገኛል፤ በዚህም ከ2003 እስከ 2008 በጀት ዓመት የተከናወኑት ነባር የመንደር ማሰባሰብ ሥራ የሚባሉ ሲሆን፣ በ2009 በጀት ዓመት የተከናወነው ግን አዲስ የመንደር ማሰባሰብ ሥራ በመባል እየተከናወነ እንዳለም ይናገራሉ።

በአዲሱ የመንደር ማሰባሰብ መርሐ ግብር ከአመራር ጀምሮ እስከ ታችኛው ፈጻሚ ድረስ እቅዱን የጋራ የማድረግ፣ ህብረተሰቡን የማሳመንና ፈቃደኛ መሆናቸውን የማረጋገጥ ሥራዎች ይከናወናሉ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ይህንን የማስተባበር ኃላፊነት አለበት። ከዚህ አኳያ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በህዳሴው ግድብ ግንባታ ምክንያት የሚነሱ 2880 አባወራ እማወራዎች እንዲሁም በጋምቤላ ክልል በአኮቦ ወረዳ 2ሺ እማወራ አባወራዎች ፤ እነዚህን 4880 አባወራ እማወራዎች ወደ ሌላ አካባቢ የማሰባሰብ እቅድ በመያዝ በተጠኑና በተመረጡ የመንደር ማሰባሰብ ማዕከላት ላይ እንዲያርፉ ሆኗል ።

በቤኒሻንጉል ክልል 2488 እንዲሁም በጋምቤላ ክልል 539 እማወራ አባወራዎችን በፍቃደኝነት በመንደር ማሰባሰብ በመቻሉ ሰዎቹ በአንድ አካባቢ ላይ ተረጋግተው በመኖር ላይ መሆናቸውን ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ወንድማገኝ አስረድተዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በነባር የመንደር ማሰባሰብ ማዕከላት ላይም ቢሆን በተለይም ከ2003 እስከ 2008 .ም በተከናወኑ ተግባራት በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች ተከናውነዋል። በዚህም በሁለቱም ክልሎች ባሉ 338 ማዕከላት 127542 እማወራና አባወራዎች ተሰባስበው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸው መረጋገጡን አመልክተዋል።

እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግም በተለይም የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ የመደገፍና የማሳደግ ሥራ እንደሚከናወን የሚናገሩት አቶ ወንድማገኝ፤ ከዚህ አኳያ በ2008 /2009 የምርት ዘመን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብቻ 458405 ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን ታቅዶ በተደረገው ድጋፍና ክትትል 419126 ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን 9ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰበ ታቅዶ 8 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማግኘት ተችሏል። በተመሳሳይ በጋምቤላ ክልልም 106497 ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን ታቅዶ 72765 ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን ከመቻሉም በላይ ከ1ነጥብ2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርትም ለመሰብሰብ መቻሉን ነው ዳይሬክተር ጀኔራሉ የሚናገሩት ።

የመንደር ማሰባሰብ ሥራው የሚከናወነው ውሃን ማዕከል በማድረግ ነው የሚሉት አቶ ወንድማገኝ፤ ከዚህም ባሻገር እንደ ትምህርት ቤት፣ የህክምና ተቋም፣ ወፍጮ ቤትና መንገድን የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች እንደሚሟሉም አብራርተዋል።

በተለይም የነባሩን መንደር ማሰባሰብ መርሐ ግብር በዋቢነት አንስተው እንደጠቀ ሱት፤ ከ2003 እስከ 2008 በጀት ዓመት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተደረገው የመንደር ማሰባሰብ ሥራ ምን ያህል ህብረተሰቡን ተጠቃሚ አድርጓል የሚለው የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል። በውጤቱም በመጠጥ ውሃ፣ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ፣ በሰውና በእንስሳት ጤና ኬላ ግንባታ፣ በአርሶ አደር ማሰልጠኛ፣ በእህል ወፍጮ እንዲሁም ማዕከላቱን የሚያገናኙ የገጠር መንገዶች ዝርጋታ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡ ተረጋግጧል።

በዚህም በአማካይ 76218 የህብረተ ሰብ ክፍሎች በአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ከመቻሉም በላይ 89 120 እማወራና አባወራዎች በማዕከላቱ ተረጋግ ተው መኖር መጀመራቸውንም ለመረዳት እንደሚቻልም ገልጸዋል።

ይህ ሁኔታ ደግሞ የልማት ጣቢያ ሠራተኞች ተረጋግተው ሙያዊ ድጋፍን እንዲያደርጉ ህብረተሰቡም በተገነቡለት ተቋማት የመጠቀም ልምዱ እንዲጨምር ከማድረጉም በላይ የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርትም ምንም ካልነበረበት አሁን እጅግ ወደ ተሻሻለ ሁኔታ ለመድረስ መቻሉን ነው የሚያመለክቱት።

ሥራው እነዚህንና መሰል ውጤቶችን ያስገኘ ቢሆንም ህብረተሰቡን የማሳመን፣ የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ግንባታ የመጓተት ችግሮች እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ ወንድማገኝ ችግሮቹን ለማለፍም ተከታታይ የህዝብ ግንኙነት ሥራዎችን በመስራት ህብረተሰቡን የማሳመን እንዲሁም የተጓተቱትን ፕሮጀክቶች በጥናት የመለየትና የመፍትሔ ርምጃ የመውሰድ ተግባር መከናወኑንም ገልጸዋል።

«ህብረተሰቡን የማሳመን ሥራ በሰፊው ተሰርታል፤ ሆኖም ህብረተሰቡ አልፈልግም ካለ በምንም መልኩ የማይገደድበትን ሁኔታ ለመፍጠር ተችሏል፤ ይህ ቢሆንም ተጠቃሚነቱ ሲረጋገጥ አንፈልግም ያሉትም አካላት ሃሳባቸውን የመቀየር ሁኔታ ስላሳዩ ተከታታይነት ያለው የንቅናቄ ሥራ በመስራት ችግሮቹን ለማለፍ ችለናል» ይላሉ።

ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚሰጡ ተቋማትን ገንብቶ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረጉ በኩልም ከአቅም ውስንነት ጋር በተያያዘ ሁሉም ጋር ማዳረስ አልተቻለም፤ ሆኖም ተከታታይ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም የክልሎቹንም አቅም በመገንባት ችግሮቹን መፍታት መቻሉን ነው የሚያብ ራሩት።

ያልተጣራ ውሃን ይጠጡ የነበሩ የህብረተ ሰብ ክፍሎች ንጹህ የመጠጥ ውሃን እንዲያገኙ ማስቻል፣ የትምህርት ቤት ደጃፍ ረግጠው የማያውቁ ህጻናትና ወጣቶች ዕድሉን እንዲያ ገኙ ማድረግ ብሎም ጤናቸው ሲጓደል የሚታ ከሙበት የጤና ኬላ ማግኘት መቻሉ ይበል የሚያሰኝ ነው። በመሆኑም በሌሎች አካባቢ ዎችም የተበታተኑ ካሉ በመንደር ተሰባስበው ተጠቃሚ መሆን ቢችሉ የተሻለ ማህበረሰብን መፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በጋምቤላ ክልል ባለፉት ዓመታት ህዝቡን በመንደር በማሰባሰብ በተሻለ መልኩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ደግሞ የተናገሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት ነሐሴ 30 ቀን 2009.ም ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት መረጃ ነው።

በክልሉ ቀደም ሲል ተበታትኖ ይኖር የነበረውን ህዝብ በመንደር በማሰባሰብ በዘላቂነት የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግ ሎቶች ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የሚናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የመንደር ማሰባሰብ መርሐ ግብሩ የፈጠራቸውን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም በተለይም በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በመንገድና በሌሎችም መሰረተ ልማት ዘርፎች ስኬታማ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አብራርተዋል።

በመንደር ማዕከላቱ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ የተሻለ የግብርና ኤክስቴንሽንና የግብዓት አቅርቦት እንዲያገኝ በመደረጉ በአሁኑ ወቅት የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል። ለዚህም በተጠናቀቀው የምርት ዘመን በመኸርና በአነስተኛ መስኖ ከለማው 105ሺ ሄክታር መሬት ከ1ነጥብ7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ርዕሰ መስተዳድሩ በማሳያነት ያነሳሉ።

እንደ አቶ ጋትሉዋክ ገለጻ፤ በክልሉ ባለፉት አሥር ዓመታት 98 የመንደር ማዕከላትን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች 180 የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመገንባታ ቸው በክልሉ ያለውን አጠቃላይ የትምህርት ቤቶች ቁጥር ወደ 346 ከፍ አድርጓል። የተማሪዎች ተሳትፎም ከ148 ሺ በላይ ደርሷል።

በሌላ በኩልም በሁሉም የመንደር ማሰባሰብ ማዕከላት የንጹህ መጠጥ ውሃና የጤና ተቋማትን በማስፋፋት ጤናማና አምራች ዜጋ እንዲፈጠር የማድረግ ሥራዎች ተከናውነዋል። በክልሉ ከአሥር ዓመት በፊት 250 ኪሎ ሜትር ብቻ የነበረው አገናኝ የጠጠር መንገድ በአሁኑ ወቅት ክልሉን ከዞን፣ ከወረዳና ከቀበሌ የሚያገናኝ 1520 ኪሎ ሜትር የአስፓልትና የጠጠር መንገድ መዘርጋቱን ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።

በጋምቤላ ከተማ ብቻ ተወስኖ የነበረው የቴሌኮምና የኤሌክትሪክ አገልግሎትም ከተወሰኑ ጠረፋማ ወረዳዎች በስተቀር በሁሉም አካባቢዎች ተዳርሶ ህዝቡ የአገልግሎቱን እያገኘ መሆኑን ገልጸዋል። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

በአሁኑ ወቅት በተለይ በግብርና ልማት፣ በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በትምህርት ጥራት እንዲሁም ድንበር ዘለል የፀጥታ ችግሮችን በመከላከል በኩል በአትኩሮት እየተሰራ ነው የሚሉት አቶ ጋትሉዋክ፤ በክልሉ ከ2000 .ም ጀምሮ ሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ በማድረግ በኩል የታዩትን መልካም ጅምሮች በአዲሱ በጀት ዓመትም ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራና እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

 

እፀገነት አክሊሉ

 

 

Published in ፖለቲካ

የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱ የማይታበል ሃቅ ነው፡፡ በተለይም የከተማዋን ዕድገት ተከትሎ የተሽከርካሪዎችና የህዝብ ቁጥር መጨመር ለትራፊክ እንቅስቃሴው ተጨማሪ ራስ ምታት ሆኗል፡፡ ታዲያ ይህ የትራፊክ እንቅስቃሴ ችግር በዋናነት በሥራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት ላይ ያይላል፡፡

ለዚህም ይመስላል በከተማዋ የትራንስፖርት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ራሱን ችሎ በአዋጅ የተቋቋመው፡፡ የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የተቋቋመበት ዋነኛው አላማውም በከተማዋ ሰላማዊ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖርና የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ነው፡፡

አሁን ያለው የከተማዋ የትራፊክ ፍሰት ምን እንደሚመስል፣ ለእንቅስቃሴው እንቅፋት ናቸው ተብለው በተለዩና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ እንዲሁም በቀጣይ በኤጀንሲው በኩል ስለታቀዱ ሥራዎች ከኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጂሬኛ ሂርጳ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የከተማዋ የትራንስፖርት እንቅስቃሴና የትራፊክ ፍሰት እንዴት ይገለፃል?

አቶ ጂሬኛ፡- የከተማዋ የትራፊክ ፍሰት በብዙ ችግሮች የተሞላ ነው፡፡ ያን ያህል ግን ተስፋ አስቆራጭም አይደለም፡፡ በከተማዋ የትራፊክ ሥርዓት ባለመኖሩ በቀጣይ የሚከሰተውን ነገር ለመተንበይ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ችግሩንም ለመቅረፍ የመንገድ ህግ መኖር አለበት፡፡ ህብረተሰቡም በእቅዱ መንቀሳቀስ የሚያስችለው የትራፊክ ሥርዓትና ፍሰት እንዲኖር እየተሰራ ነው፡፡ የመንገዶች ሁኔታም ሥርዓት እንዲይዙ ይደረጋል፡፡ ቀደም ሲል ዋነኛ ትኩረታችን የነበረው መንገድ ግንባታ ላይ ብቻ በመሆኑ የትራፊክ ማኔጅመንት የተረሳ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በተለይም በከተማዋ መንገዶችን በብዛት መገንባትና ማስፋት ሲጀመር የትራንስፖርት እንቅስቃሴው ችግር እየጎላ መጥቷል፡፡ ለትራፊክ እንቅስቃሴው አዋኪ የሆኑ ነገሮችን ማጥፋት፣በደንብ ማስከበርና በቴክኖሎጂ የታገዘና ትክክለኛ የመንገድ ህጎች እንዲኖሩና ህጎቹም እንዲከበሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የመንገድ ተጠቃሚውም ብዙ አማራጭ እንዲኖሩትና ግራ የሚያጋባ የመንገድ ሥርዓት እንዳይኖር በማድረግ እንቅስቃሴውም ሥርዓት የያዘ እንዲሆን ማድረግ የትራፊክ ማኔጅመንት ሥራ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅትም እየተስተዋለ ያለው የትራፊክ እንቅስቃሴ ችግር ቀደም ሲል የተከማቸ ነው፡፡በመሆኑም ዘለቄታዊ መፍትሔን ለማምጣት የትራፊክ ማኔጅመነት ኤጀንሲ ተቋቁሟል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኤጀንሲው ከተቋቋመ በኋላ የተሰሩ ዋና ዋና ተግባራት ምንድን ናቸው?

አቶ ጂሬኛ፡- ኤጀንሲው ከተቋቋመ ሁለት ዓመት ቢሆነውም በከተማዋ ከትራፊክ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የሚታዩ አንገብጋቢ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት አድርጓል፡፡ ህብረተሰቡ ረጅም ሰዓታትን በጉዞ የሚቆምባቸውን ማጋጠሚያ ቦታዎችንና አደባባዮችን የማሻሻል ሥራዎች አከናውኗል፡፡ ለአብነትም ጀሞ ሚካኤል፣ ቦሌሚካኤል፣ ኮልፌ18ማዞሪያ፣ኢምፔሪያልና ጀርመን አደባባይ በቀለበት መንገድ መጋጠሚያ ላይ የሚገኙና ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት የሚያስተናግዱ በመሆናቸው የማሻሻልና ተሽከርካሪዎች በአደባባይ እንዲስተናግዱ የማድረግ ሥራ ተከናውኗል፡፡

በቄራ እና በሰዓሊተ ምህረት አካባቢ ተንቀሳቃሽ የትራፊክ መብራቶችን በመትከል የትራፊክ ፍሰቱ የተሻለ እንዲሆን ከማድረግም ባሻገር በእግረኞች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ መገናኛ፣ሜክሲኮና ስታዲየም አካባቢዎች ላይ የፕላስቲክ አጥሮች በማጠር እግረኞች ወደ ተሽከርካሪ መንገድ እንዳይገቡ የማድረግ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ይህ ሁኔታም የመንገድ አጠቃቀሙ በሥርዓት እንዲመራ ረድቷል፡፡

የትራፊክ እንቅስቃሴው የበለጠ የተሳለጠ እንዲሆን በመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ልማት ላይ ባለሀብቶችን በማሳተፍ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ በሌላ በኩልም ደንብ የማስከበር ሥርዓቱን በማጠናከር እግረኞችም ሆኑ አሽከርካሪዎች የመንገድ ህግ አክባሪ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የትራፊክ ፍሰቱን የሚያጨናንቁ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎችም በአምስቱም የከተማዋ መውጫና መግቢያዎች ላይ ከጠዋት 1 ሰዓት እስከ 3 ሰዓትና ከሰዓት ከ10 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ወደ መሀል ከተማ እንዳይገቡ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የትራፊክ እንቅስቃሴውን አዋኪ ከሆኑ ነገሮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት የትኞቹ ናቸው?

አቶ ጂሬኛ፡- ለትራፊክ እንቅስቃሴው ጤናማ አለመሆን በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከእነዚህም መካከል ህብረተሰቡ ለመንገዶች ያለው ገንዛቤ አናሳ መሆን፣ መንገዶችን ለተለያዩ አላስፈላጊ ነገሮች መጠቀም ለምሳሌ ለህንጻ ግንባታ የሚሆኑ አሸዋና ጠጠር ማፍሰሻ ማድረግ፣ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖር፣ የእግረኛ መንገዶች ግንባታ ያለመጠናቀቅ በእግረኛ መንገዶች ላይ የሚካሄዱ የስልክና የመብራት ዝርጋታዎች በተናበበ መልኩ አለመሄድ፣ የመንገድ ላይ ህገ ወጥ ንግዶችና የመንገድ ዳር የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች በደንብ ያለመሰራት በተለይም በክረምት ወቅት መንገዶች በውሃ እንዲሞሉ በማድረግ የትራፊክ ፍሰቱን ያውካሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ችግሮቹን ለመፍታት ምን እየተሰራ ነው ?

አቶ ጂሬኛ፡- የትራፊክ ፍሰትን ለማሻሻል መንገዱና የመንገድ ተጠቃሚው አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡ የትራፊክ ማኔጅመንትን ከባድ የሚያደርገው ለችግሩ አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ምክንያቶች ብዙ መሆናቸው ነው፡፡ በመሆኑም የእግረኛ መንገድ ሲዘረጋ የኤጀንሲው ደንብ ማስከበር አካል ከመንገዶች ባለስልጣን ደንብ ማስከበር ጋር በመሆን ቦታዎችን በመለየት እንዲነሱ ያደርጋል፡፡ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን ለመገንባት ባለሀብቶችን ተሳታፊ በማድረግ ተጨማሪ ጥናቶች እየተካሄዱ ናቸው፡፡ ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም በመቀናጀት እየተሰራ ይገኛል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የትኞቹ የከተማዋ ክፍሎች በከፍተኛ ደረጃ የትራፊክ መጨናነቅ ይስተዋልባቸ ዋል? ምንስ እየተሰራ ነው?

አቶ ጂሬኛ፡- በከተማዋ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ የነበረበት በርካታ ተሽከርካሪዎችን በሚያስተናግዱ የቀለበት መንገዶችና ማጋጠሚያዎች ላይ ነው፡፡ በቀለበት መንገዱ ላይ ያሉ አንዳንድ አደባባዮች ተሽከርካሪዎችን ለማስተናገድ ያላቸው አቅም አነስተኛ መሆን ለትራፊክ መጨናነቁ ተጨማሪ መንስኤ ነው፡፡

በአጠቃላይም በኤጀንሲው በተጠና ጥናት 27 የሚሆኑ መጋጠሚያዎች ላይ ጥናት የተደረገ ሲሆን፣ በተጨማሪም የትራፊክ ፍሰት ቆጠራና የፍጥነት ወሰን ቁጥጥር ይካሄዳል፡፡ በዚህም የትራፊክ አደጋ የሚበዛባቸው ቦታዎች ይለያሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በሥራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት ላይ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ይከሰታል፡፡ የችግሩ መንስኤ ምንድን ነው? መቼስ ነው የሚፈታው?

አቶ ጂሬኛ፡- ይህ ጉዳይ ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ወደ ከተማዋ በየጊዜው እየፈለሰ የሚመጣው ህዝብ ቁጥር መጨመርም የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ በመሆኑም ይህ ጉዳይ እንደአገር ትልቅ አጀንዳ ሆኖ መሰራት አለበት፡፡ ምክንያቱም ችግሩንም ጥቅሙንም ያልተማከለ ከማድረግም ባሻገር ለአሰራርም ቀላል ይሆናል፡፡ ኤጀንሲው በዋናነትም በትራፊክ እንቅስቃሴው ችግር ምክንያት የሚመጡ ተፅዕኖዎችን ከመቀነስ አኳያ ይሰራል፡፡

ሁሉም የመንግሥት መስሪያ ቤቶችና ትምህርት ቤቶች የሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት እኩል መሆን ለትራፊክ መጨናነቁ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ በቀጣይ በግልና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በመንግሥት መስሪያ ቤቶች የመግቢያና መውጫ ሰዓት በመለያየት ችግሩን መፍታት ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- አደባባዮችን በመብራት የመቀየር ሥራዎች ለትራፊክ እንቅስቃሴው ምን አስተዋፅኦ አበረከተ?

አቶ ጂሬኛ፡- በአውስትራሊያ የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂዋ ውስጥ በርካታ አደባባዮችን በትራፊክ መብራት እንዲቀየሩ በማድረግ ውጤታማ ሆናለች፡፡ በአዲስ አበባ ከ80 በላይ የሚሆኑ አደባባዮች ይገኛሉ፡፡አደባባዮች ያልተገባ ቦታ ሲገነቡ ወይም ደግሞ ከአቅማቸው በላይ ተሽከርካሪዎችን ለማስተናገድ ሲቸገሩና በትራፊክ እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በመሆኑም አደባባዮቹ በትራፊክ መብራት እንዲቀየሩ ይደረጋል፡፡ በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች የተገነቡ አደባባዮች በትክክል ዲዛይን ተደርገው ባለመሰራታቸው ችግር ሲፈጥሩ ይስተዋላል፡፡ በመሆ ኑም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ተገንብተው የነበሩ አደባባዮች ፈርሰው በትራፊክ መብራት መተካታቸው ጥሩ ለውጥ አምጥቷል፡፡ የትራፊክ ማኔጅመንት ሥራ ተለዋዋጭ ከመሆኑ አንፃር በየጊዜው የትራፊክ እንቅስቃሴውን ለማሻሻል የተለያዩ ዘዴዎችን በመቀየስ ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡ አሁን የመጣውን የተሻለ የትራፊክ እንቅስቃሴ ለውጥ በቀጣይም ለማስቀጠል አደባባዮችን በማፍረስ በመብራት የመተካት እቅዶች ተይዘዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ከኤጀንሲው ምን ይጠበቃል?

አቶ ጂሬኛ፡- የትራፊክ እንቅስቃሴው ሥርዓት እንዲኖረው በቀጣይ በከተማዋ ወደ 31 የሚሆኑ የትራፊክ መብራቶች ይተከላሉ፡፡ ይህም ተግባራዊ ሲሆን ለትራፊክ እንቅስቃሴው አስቸጋሪ የሆኑ የመንገድ መጋጠሚያዎች እየቀነሱ ይመጣሉ፡፡ በተለይም ዋና መንገዶች ትክክለኛ አገልግሎታቸውን እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ የትራፊክ ማኔጅመንት ማዕከልም ይቋቋማል፡፡ ፕሮጀክቱም በዋናነት ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በከተማዋ ወደ 135 የሚጠጉ የመንገድ መጋጠሚያዎ ችን በማጥናት ማሻሻያ ይደረጋል፡፡ አንድ ቦታ በመሆን የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት ለማየት የሚያስችል ቴክኖሎጂም በእቅድ ተይዟል፡፡ በአጠቃላይ የከተማዋን የትራፊክ ሥርዓት የማዘመን ሥራ ይሰራል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?

አቶ ጂሬኛ፡- የትራፊክ ማኔጅመንት ሥራ በጣም ውስብስብ ከመሆኑ አኳያ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንገድ ተጠቃሚውም ትክክለኛ የመንገድ ህጎችንና ደንቦችን በማክበር መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ የተለያዩ ተቋማት የመገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ትክክለኛ የመንገድ አጠቃቀም ሥርዓትን ከማስተማር አንፃር ቅንጅታዊ ሥራ መስራት ይጠበቅባቸ ዋል፡ ይህ ከሆነ በከተማዋ የትራፊክ ፍሰቱ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ኤጀንሲው የትራፊክ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ይፈታዋል ማለት አይደለም፡፡ በመሆኑም በጋራ መስራት የግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በትራፊክ ማኔጅመንት የሚታዩ የተወሰኑ ለውጦች በመኖራቸው በቀጣይ ዓመታት የተሻሉ ለውጦች ይኖራሉ፡፡ አዲስ አበባም በአምስት ዓመታት ውስጥ ዘመናዊ የትራፊክ ፍሰት ሥርዓት እንደሚኖራት ይጠበቃል፡፡

 

አስናቀ ፀጋዬ

Published in ኢኮኖሚ

በአሜሪካ የመሣሪያ ቁጥጥር ህገ ደንብ አነጋጋሪ መሆኑን ቀጥሏል፤

 

የአሜሪካ ሕገመንግሥት የነፃነት ቀንዲል ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደአርአያ ይነሣል፤ ይወደሳል፡፡ እ..1789 በወጣው በዚህ ሕገ መንግሥት የመብቶች ድንጋጌ ሁለተኛው ማሻሻያም ሰዎች መሣሪያ የማግኘትና የመያዝ መብት እንዳላቸው ማረጋገጫን ይሰጣል። በዚህም ምክንያት በልዕል ኃያል አገር የነፍስወከፍ ጦር መሣሪያ ገበያ (የጠመንጃና ሽጉጥ ገበያ) ለሁሉም ክፍት ነው። መሣሪያ የሚሸጡም ሆነ የሚገዙ ሰዎችን ቁጥርም በየጊዜው የሚጨምር እንጂ የሚቀንስ አይደለም።

መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም አገሪቱ ከ 3 ሚሊዮን በላይ የነፍስወከፍ ጦር መሣሪያ አላት። ይህም አንድ ግለሰብ ከአንድ በላይ መሣሪያ አለው እንደማለት ነው። የመሣሪያ ንግዱ በሚጦፍባት በዚህች አገር ግን የጦር መሣሪያ ሽያጭ መቆጣጠር የሚያስችል ሕግ የለም። በዚህም ምክንያት በየጊዜው በመሣሪያ የታገዘ ሁከትና ጥቃት ይፈፀማል። በክስተቱም ዜጎች ይሞታሉ። በጅምላ ይጨፈጨፋሉ። ብዙዎች ያለቅሳሉ። ውስጣቸውም ይደማል።

በአገሪቱ ድንገተኛ የጦር የመሣሪያ ጥቃት ሲፈፀም የመሣሪያ ባለቤትነት ሕግ ደንብ ሁሌም ቢሆን ወቅታዊ መነጋጋሪ ይሆናል። ወሬውም ለአንድና ሁለት ሳምንታት ከተወራ በኋላ የውሃ ሽታ ሆኖ ይቀራል። ተቃዋሚዎች፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ ጋዜጠኞችም ወደ ሌላ ወሬ ይሸጋገራሉ።

የሕይወት ጥፋትና ሁከት ረገድ አሜሪካ በዓለም የመጀመሪያውን ደረጃ ትይዛለች። በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጦር መሣሪያ አማካይነት የሚፈጸም ሁከትና ጥቃት ወረርሺኝ ሆኗል። እንደ ዘጋርዲያን የሰሞኑ ዘገባም በአገሪቱ በ 1 735 ቀናት ውስጥ 1516 የጅምላ ተኩስ ተፈፅሟል።

በቅርቡ ታሪክ ስናስታውስ እንኳን በላስ ቬጋስ የሙዚቃ ኮንሰርት በታደሙ ሰዎች ላይ ስቴፈን ፓዶክ የተባለ የ64 ዓመት ታጣቂ በተፈፀመ ጥቃት ከ59 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከ 500 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል። ቁማርተኛና የቀድሞው የሂሳብ አያያዝ ባለሙያ እንደሆነ በተነገረለት ግለሰብ የተፈፀመው ጥቃትም በኦርላንዶ 49 ሰዎች ከሞቱበትና በወቅቱ የከፋ ከተባለው አደጋ ልቆ በአሜሪካ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ከተፈጸሙት ሁሉ በላይ ደም አፋሳሽ ሆኗል።

አገሪቱ ምንም ልዕል ኃያል ብትሆንም ለመሰል ጥቃቶችንም እልባት መስጠት አልቻለችም። የሰላማዊ ሰዎች እልቂት ለመቆጣጠር የሚያስችልና መሣሪያ የመያዝ (የመግዛት) እንዲሁም በባለቤትነት ነፃነት ላይ ገደብ የሚጥል ጠበቅ ያለ ፖሊሲና ሕግ የማውጣት አቅምም አጥታለች።

በእርግጥ በጦር መሣሪያ አማካይነት የሚፈጸም ሁከትና ጥቃት አሜሪካ ውስጥ ብቻ የሚፈፀም አይደለም። በሌሎች አገራትም ይከሰታል። ይሁንና ሌሎች አገራት መሰል ጥቃት ሲያስተናግዱም ሆነ ከማስተናገዳቸው ቀድመው በጦር መሣሪያ ባለቤትነት ላይ ጠንካራ ሕግ አውጥተዋል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሆና የምትጠቀሰው ደገሞ አውስትራሊያ ናት።

አውስትራሊያ እ..1996 በቱሪስቶች መንደር ለ 35 ሰዎች ሞት እንዲሁም ለ 28 በላይ ሰዎች ጉዳት ምክንያት የሆነውን የጅምላ ጭፍጨፋ ተከትሎ በመሣሪያ ቁጥርና ባለቤትነት ላይ ጠበቅ ያለ ሕግና ፖሊሲ አርቅቃለች። በዚህም ተጨባጭ ለውጥ አምጥታለች። በርካታ አገራትም የአውስትራሊያን ፈለግ በመከተል የጦር መሣሪያ የመያዝ (የመግዛት) መብትን የሚያጠናክሩ ሕጐችን አሻሽለዋል። አውስትራሊያ ያመጣችውን ለውጥ ለማምጣት አሜሪካ ብዙም ወጪና ድካም አይጠይቃትም። ዋናው የፖሊሲ ምርጫና ጠንካራ ሕግ የማርቀቅ ጉዳይ ነው።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአገራቸው ውስጥ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን በጦር መሣሪያዎች አማካኝነት የሚፈፀመውን የሰላማዊ ሰዎች እልቂት የመቆጣጠር ድክመት መወገድ እንዳለበት ሲወተውቱ ቆይተዋል። «የጦር መሣሪያ ሕግ ሊወጣና መሣሪያ በመያዝና በባለቤትነት ነፃነት ላይ ገደብ ሊጣል ይገባል» የሚል አቋማቸው ለማሳመን እንባ አውጥተው እስከመማፀን ብዙ ጥረዋል።

የመሣሪያ ሻጮች የኋላ ታሪክ እንዲመረመር፣ ግዛቶች በቤተሰብ ውስጥ ሁከትን በመፍጠርና በአዕምሮ ሕመም ምክንያት የጦር መሣሪያ እንዳይገዙ ዕገዳ ስለተደረገባቸው ሰዎች ኢንፎርሜሽን እንዲያስተላልፉ፣ በእነዚህ አቅጣጫዎች የሚደረገውን ቁጥጥር ለማቀላጠፍ የአሜሪካ ምርመራ ፌዴራል ቢሮ (ኤፍቢአይ) በሠራተኞች ይበልጥ እንዲደራጅ ጠይቀዋል።

የአገሬው ኮንግረስ ግን ለዚህ የፕሬዚዳንቱ ተማፅኖና ጥያቄ የሰጠው ምላሽ ዝምታ ነው። በዚህ የኮንግረሱ ዝምታ አሁንም ድረስ እንደ ቬጋሱ ዓይነት አሰቃቂ ጥቃቶች መፈፀማቸውን ቀጥለዋል። የቬጋሱ ጥቃት ግን ከሁሉ በላይ በአሜሪካ የጦር መሣሪያ አያያዝና ባለቤትነት ሕግ ላይ ጫና ክርክርና መረር ያለ ወቀሳን ይዞ ብቅ ብሏል።

በተለይም ልዕል ኃያሏ አገር መሰል የሰላማዊ ሰዎች እልቂት ለመቆጣጠር የሚያስችልና መሣሪያ የመያዝ (የመግዛት) እንዲሁ በባለቤትነት ነፃነት ላይ ገደብ የሚጥል ጠበቅ ያለ ፖሊሲና ሕግ የማውጣት አቅም ለምን አጣች? የሚል ጥያቄ ተነስቷል። በዚህ ረገድ ሃሳባቸውን የሚያጋሩ የፖለቲካ ምሁራንና የመገናኛ ብዙኃን ጸሐፍት ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሉትን አጋርተዋል።

በተለይ እንደ ሲኤን ኤን የፖለቲካ ጉዳዮች ፀሐፊውው ክሪስ ሲሊዛ ትንታኔ፤ በአሜሪካ ከአስር ሰዎች አራቱ በቤታቸው ጦር መሣሪያ አለ።74 በመቶ የአገሬው ዜጎችም መሣሪያ በቤታቸው በመኖሩ ብቻ ነፃነት ይሰማቸዋል። መሠረታዊ መብትና ነፃነታቸው መሆኑንም ያምናሉ። ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የአገሬው ዜጎች መሣሪያ የመያዛቸውን ዋነኛ ምክንያት ሲያስረዱ ለአደን ግልጋሎት የሚል መልስ ይሰጡ እንደነበር የሚያስታውሰው ፀሐፊው፤ አሁን ላይ ዜጎች መሣሪያ የሚይዙበት ዋነኛ ምክንያት ግን ስጋት መሆኑን ያስረዳል።

እንደ ፀሐፊው ገለፃ፤ ከሕዝቡ በተጓዳኝ የአገሬው ፖለቲከኞች በጦር መሣሪያ ላይ ያላቸው አመለካከት ለየቅል ነው። ከሦስቱ የሪፐብሊካን ፓርቲ አቀንቃኞች መካከል አንዱ ብቻ ጦር መሣሪያ የአገሪቱ ዋነኛ ችግር መሆኑን ያምናል። ጦር መሣሪያን በቀላሉ ማግኘት መቻልም የጅምላ ጭፍጨፋ መነሾ ሊሆን እንደማይችል ያስባሉ። ይህም አገሪቱ የጦር መሣሪያ ሕገ ደንቡን እንዳትተገብር ማነቆ ሆኖባታል።

ይህ ብቻ ግን አይደለም። በጦር መሣሪያ ላይ የመንግሥት አቋም ምን መሆን አለበት በሚለው እሳቤ ላይ በእጅጉ የተቃረነ አመላካከት ይስተዋላል። በመሣሪያ ቁጥጥር ደጋፊዎች ሕግ ያስፈልገዋል በሚል የፍትህ ያለ ሲሉ ተቃዋሚዎች በአንፃሩ ሰዎች ሕግ ደንብ ማውጣት መፍትሄ እንደማይሆን እምነት አላቸው።

በተለይ የአገሬው ፖለቲከኞቹ በሕጉ ላይ ያላቸውን አቋም ግራና ቀኝ ነው። ዲሞክራቶች የመሣሪያ ባለቤትነት ቁጥጥሩ መጠናከር እንዳለበትና ለዚህም ሕገ ደንብ ሊዘጋጅለት እንደሚገባ እምነት አላቸው። ሪፐብሊካኑ በአንፃሩ በተቃራኒ አቅጣጫ ቆመዋል። የፖለቲካ ምሁራኑ እንደሚተቻቸው ከሆነም ፤ሪፐብሊካኑ ክክስተቱ በኋላ ኀዘናቸውን መግለፅና መፀለይን ምርጫቸው ከማድረግ በዘለለ ስለ ሕጉ ተግባራዊነት ቃል አይተነፍሱም።

ሌላኛው የሲ ኤን ኤን ፀሐፊ ስቴቨን ኮሊንሰን አሜሪካ ሕጉን ለተግባራዊ ለማድረግ የሰነፈችበት ምክንያት አሁንም ቢሆን የሕጉ ተግባራዊነት አጠራጣሪ መሆኑን ሲያስረዳ እንደሚገልፀው፤ ሪፐብሊካን በነጩ ቤተ መንግሥትና በኮንግረሱ ያለውን የሥልጣን ኃይል ጠቅልለውታል። ይህ እንደመሆኑም የዲሞክራቶቹ ፍላጎት ተፈፃሚነት ዝቅተኛ ነው» ይላል።

እንደ ፀሐፊው ሀተታም፤«ናሽናል ራይፍል አሶሲየሽን» የሚል ስም የሚታወቀው የጦር መሣሪያ ሻጮች ማህበርም በሪፐብሊካኑ የፖለቲካ ምህዋር ላይ ያለው ሚና ከባድ ነው። ይህ ማህበር ደግሞ ለሕጉ ተፈፃሚነት በተፃራሪነት የቆመ ነው። ከባራክ ኦባማ በተሻለ ዶናልድ ትራምፕ ሕገ ደንቡን ለማዘጋጀት ዛሬም ድረስ ዳተኛ የሆኑትም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ማረጋገጥ አይከብድም።

ቮክስ ኒውስ የፖለቲካ ጉዳዮች ፀሐፊ ጀርማን ሎፔዝ እንደሚገልፀው፤ አሜሪካ ከሌሎች አገራት ሲነፃፀር የመሣሪያ ቁጥርም ሆነ በጦር መሣሪያ አማካኝነት በሚፈፀም ቀውስ የሚስተካከላት የለም። በአንድ አገር ብዙ መሣሪያ አለ ማለት ብዙ ቀውስና ሞት አለ እንደማለት ነው። እናም የመጀመሪያ ተግባር መሣሪያዎች መቀነስና ዜጎችን መሣሪያ በቀላሉ ማግኘት እንዳይችሉ ማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ ጠንካራ የመሣሪያ ሕግ ማርቀቅ ይገባል። ይሁንና የአገሪቱ ሕግ አውጪዎች ይህን ማድረግ አልቻሉም። ይህ ቢያደርጉ የሰሞኑን የቬጋስ የጅምላ የተኩስ ጥቃት ማስቆም ይቻላቸው እንደነበር መረዳት ትክክለኛነት ነው።

መሰል ቀውስ ዳግም እንዳይከሰት ለጉዳዩ ፖለቲካዊ አንድምታን መስጠት ይገባል የሚል አቋሙን የሚያስረዳው ፀሐፊው፤ ፖለቲካ ማለት በሌላ ገለጻ የሕግ ተፈፃሚነት ነው፤ የጅምላ የጦር መሣሪያ ጥቃት ማለት አንድ ሁነት ነው፤ የተጠናከረ ሕግና ፖሊሲ በእጅጉ ሊቀንሰው የሚችል ነው፤ መሰል ቀውሶች እልባት የመስጠት የመንግሥትና የፖለቲካ ሥርዓቱ ኃላፊት ነው» ይላል።

እንደ ፀሐፊው ገለፃ፤ መንግሥት ግለሰቦችና ተቋማት በግል መፍታት ያቃታቸውን ችግሮች የሚፈታ አካል ነው። አንድ እስከፊ ክስትት ሲፈፀም መንግሥት አፋጣኝ ውሳኔ በመውሰድ ዳግም እንዳይከሰቱ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። በመሆኑም ይህን ችግር ከወዲሁ አልባት ለመስጠት የፖለቲካ አስተዳደሩ መሰል ቀውስን የማስወገድ ኃላፊነት መወጣት ይኖርበታል። ፖለቲከኞችም በምርጫ ቅስቅሳው ወቅት መሰል ችግሮችን ለማስቆም የገቡትን ቃል ሊያክብሩ ይገባል። ምክንያትም የመረጥናቸው ቃል ስለገቡልን ነው።

«እናም የአገሬው ሕዝብ ጉዳዩን ፖለቲካዊ አንድምታ ሊሰጠው ይገባል፤ ይህን እስካላደረገ ለውጥ ማምጣት አይችልም። ምክንያቱም እስካሁን እየተፈፀሙ የሚገኙ ጥቃቶች በሙሉ የመንግሥት የቸልተኝነት ውጤት ናቸው» በሚል ሃሳቡን ይጠቀልላል።ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን «በሕጉ ላይ መነጋገር ካስፈለገን የምንነጋገር በት ጊዜ አሁን አይደለም» የሚል አቋም ይዘዋል።

አንዳንዶች ግን በቂና በርካታ መሣሪያ ባለበት አገር ጠንካራ ሕግ ማርቀቅ ከተቻለ ቀውሱን ማስቆም ይቻላል ሲሉ ገሚሶቹ፤ የሕግ ማዕቀፍ ቢዘጋጅም መጥፎ ሰዎች መጥፎ ከማድረግ እንደማይቆጠቡ ይናገራል። እንደእሳቤው ደጋፊዎች እምነትም፤ የመሣሪያ ባለቤትነት ብቻውን ችግር አይደለም። ዋናው ዜጎች መሣሪያውን ለምን ግልጋሎት እንደፈለጉት ማወቅ ነው። እናም መንግሥት ማጤን ያለበት መሣሪያው ላይ ሳይሆን ሰዎች በመሣሪያውን በክፉ እሳቤ ለመጠቀም የሚያነሳሳቸው ተዋጽኦ ላይ ነው። አገሪቱ መስራት ያለባትም ይህን ነው የሚል አቋም ይዘዋል።

የለም የለም መሰል ጥቃቶች የሚፈፀሙት ከመሣሪያው ጀርባ የአደንዛዥ እጾች ቁጥጥር ላይ ያለመስሯቷ ውጤት ነው፤ ብዙዎች መሣሪያ በቀላሉ ማግኘት እንዳይችሉ የሚገድብ ጠንካራ ሕገ ማዕቀፍ መኖሩ መልካም ቢሆንም መሰል ጥቃቱን ለማስቆም አገሪቱ አደንዛዥ እጾችን የመቆጣጠር ትግበራን ዳግም ማጤን ይገባታል ሲሉ የሚወተውቱም አልጠፉም። አሁን ላይ የመሣሪያ ቀውስ ለአሜሪካ ከባድ ራስ ምታት ሆኗል «በዚህ አጋጣሚ መነሾ አንድ እርምጃ መሄድ ካልተቻለ ለአገሪቱ የሚቀራት ጠባሳ ጎልቶ የሚታይ ይሆናል» የሚሉት ግን ለውጥን ይማፀናሉ።

 

ታምራት ተስፋዬ

 

 

Published in ዓለም አቀፍ

 

ኢትዮጵያ ድርቅን ለመከላከልና ድርቅ በሚያጋጥማት ወቅትም ከተረጂነት ለመላቀቅና ራሷን ችላ ከችግሩ ለመውጣት አቅሟን እያዳበረች ትገኛለች፡፡ ይህ የሆነውም የግብርና ምርትንና ምርታማነቷን ማሳደግ በመቻሏ ነው፡፡ ይህ የተፈጠረ አቅም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መላው የአገራችን ህዝብ ግብርናን በማዘመን፣ የተፈጥሮ ሃብትን በመጠበቅ እንዲሁም በመንከባከብና ለአፈር እና ለውሃ ጥበቃ የተሰጠውን ትኩረት ማጎልበት ይኖርበ ታል፡፡

እስካሁን ድረስ የተደረጉ ጥረቶች አገራችን ውስጥ የተፈጠሩ የድርቅ አደጋዎችን መቋቋም የቻሉ ናቸው። እንደሚታወቀው ከታዳሽ ኃይል በተለይም ከውሃ ኃይልን በማመንጨት በአንጻራዊነት ከሌሎች አገራት ቀድማ አረንጓዴ ልማትን መተግበር የጀመረችው ኢትዮጵያ፣ ሀገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ያላትን ተጋላጭነት ለመቋቋም የአረንጓዴ ልማት ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ መቅረጿ አይዘነጋም፡፡

ከአረንጓዴው ልማት ስትራቴጂ መሰረቶች ውስጥ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን፣ የደን ልማት፣ ታዳሽ ኃይል አማራጭ መከተል እንዲሁም የትራንስፖ ርት፣ የኢንዱስትሪ የቤት ልማትን በተስማሚ ቴክኖሎጂ መተግበር የሚሉት ጉዳዮች በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው።

የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ፣ ኢትዮጵያ ያቀደችውን የተለጠጠ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳካትና የሙቀት አማቂ ጋዞችን መቀነስ የሚያስችሉ አማራጮችና ዕድሎችን መለየት ዋናው አላማው ነበር፡፡ መንግሥት በዘርፉ የተሻለ ልምድ ያላቸውን የልማት አጋር አካላትን ለመሳብ ጥረት እንደሚያደርግም ስትራ ቴጂው ያመለክታል፡፡

የልማቱ አማራጭ አብዛኛውን የአገሪቱን ጠቅላላ ምርት ነዳጅና ተመሳሳይ የኃይል ምንጮችን ከውጭ በማስገባት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ አገሪቱን ለውጭ ምንዛሪ እጥረት ይዳርጋታል፡፡ ከታዳሽ ኃይል በተለይም ከውሃ ኃይልን በማመንጨት በተነጻጻሪ ከሌሎች አገራት ቀድማ አረንጓዴ ልማትን መተግበር የጀመረችው ኢትዮጵያ፣ አገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ያላትን ተጋላጭነት በፍጥነት የአረንጓዴ ልማት ማስፈጽሚያ ስትራቴጂ ቀርጻለች፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን፣ የደን ልማት፣ ታዳሽ ኃይል አማራጭ መከተል እንዲሁም የትራንስፖርት፣ የኢንዱስትሪ የቤት ልማትን በተስማሚ ቴክኖሎጂ መተግበር የአገሪቱ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂው መሰረቶች ናቸው፡፡ የስትራቴ ጂው መሰረቶች አተገባበር እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

የመጀመሪያው የስትራቴጂው መሰረት የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን ነው፡፡ ዘርፉ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሪ መሆኑና የአብዛኛው ዜጎች መተዳደሪያ መሆኑ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ ከዚህ ቀደም በተለምዶ እንደሚደረገው የሚታረስ መሬትን ማስፋፋትና የቀንድ ከብቶችን ቁጥር ከማሳደግ ይልቅ የመሬትንና የቀንድ ከብቶችን ምርታማነት ማሳደግ የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫ ነው፡፡

የተሻሻሉ የሰብልና የቀንድ ከብት ዝርያዎችን አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ማድረግ የግብርና ዘርፍ ማሳደጊያ ስልት ነው፡፡ የደን ጭፍጨፋን ለመቀነስ በተለ ይም በተራቆቱና በተጎዱ አካባቢዎች ዝቅተኛ፣ መካከለኛ እንዲሁም ከፍተኛ የመስኖ ልማት ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት ጥረት ተደርጓል፡፡ እነዚህ ጥረቶች ድርቅን የመቋቋም አካል ናቸው፡፡

እርግጥ በተፈጥሮ የአየር መዛባት ምክንያት በሀገራችን የድርቅ አደጋ ሲከሰት አዲስ ነገር አይደለም። ይህ ደግሞ በተፈጥሮ ችግር ምክንያት የሚከሰት ጉዳይ በመሆኑ ምንም ማድረግ አይቻልም። ሆኖም ይህ በየጊዜው ሀገራችንን የሚጎበኛት የድርቅ አደጋ ወደ ረሃብነት እንዳይቀየር መንግሥት ብርቱ ጥረት አድርጓል።

እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት የመንግሥት ትኩረት ምንም ዓይነት የአየር ንብረት መዛባትና ድርቅ ቢያጋጥም፤ ህዝባችን የማይራብበት ሁኔታን በመፍጠር ላይ ሲረባረብ መቆየቱ አይዘነጋም። የኤልኒኖ አደጋ በተከሰተበት ወቅትም አደጋውን በመቀልበስ የልማት አጋር ሀገራትን ድጋፍ እምብዛም ሳያገኝ ችግሩ ወደ ረሃብነት ሳይቀየር መቋቋሙ ይህን ጥረቱን አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን ከማንም የተሰወረ ጉዳይ አይመስለኝም።

በእኔ እምነት መንግሥት ከአጭር ጊዜ አኳያ በተፈጥሮ ችግር ምክንያት የሚከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል በፍጥነት በመድረስና ዕርዳታ ማድረግ እንዲሁም ድጋፉ ልማታዊ በሆነ አኳኋን ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጉ ለዜጎቹ ያለውን የኃላፊነትና የተጠያቂነት መንፈስ ስሜትንና ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ነው።

አርሶ አደሩ ከራሱ ተርፎ ለገበያ በማምረት ተጠቃሚ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ አገሪቱም ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ጎዳና እንዲፈጠር አድርጓል። ለዚህ ስኬት በመንግሥት በኩል የተወሰዱት እርምጃዎች በቂ ማሳያዎች ናቸው ማለት ይቻላል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ ለእርሻ የሚውል ሰፊ መሬት አላት። ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች በአርሶ አደሩ እጅ እንዳለ የሚታሰበው መሬት አነስተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ካለችውም መሬት ቢሆን የሚያገኘው ምርት ዝቅተኛ ነው። አመራረቱም እጅግ ኋላ ቀር ሆኖ ቆይቷል።

ይህን ዕውነታ የተገነዘበው የኢፌዴሪ መንግሥት ዘርፈ ብዙ የማሻሻል ጥረቶች አድርጓል። በውጤቱም አነስተኛ ይዞታ ባላቸው አነስተኛ የአርሶ አደሮችን ማሳ ላይ ለውጥ ማምጣት አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ ሰብሯል። አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ለሰፋፊ እርሻዎች ትኩረት መስጠትና ለውጥ ማምጣትን የሚሰብኩ ወገኖችን አፍ ማስያዝ የቻለ ትክክለኛ መስመርን በመከተል ውጤት ማምጣት ችሏል።

በአርብቶ አደሩም አካባቢ ተመሳሳይ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በመቅረፅና ቀደ ተግባር እንዲገባ በማድረግ ድርቅ ሊፈጥር የሚችለውን አደጋ በአያሌው መቀነስ ተችሏል። ከእነዚህ መንግሥታዊ ጥረቶች ውስጥ የአርብቶ አደር የልማት ፓኬጆችን በመቅረፅ ውጤታማ ሥራ ተከናውኗል።

አርብቶ አደሩ ከልማዳዊ የአኗኗር ባህል ወጥቶ ወደ ዘመናዊ ህይወት እንዲቀየር፣ ከአርብቶ አደሩ ጋር በመነጋገር ድርቅን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችሉ የመስኖ ልማት ሥራዎችን በማስፋፋት ወደ ከፊል አርሶ አደርነት እንዲሸጋገር ብሎም ምርጥ ዝርያዎችን አግኝቶ ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ፣ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃዎችን በአግባቡ የማሰባሰብ ሥራዎችን እንዲያጠናክርና ሌሎች መሰል ተግባራቶች ተከናውነዋል።

ሆኖም አሁንም ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም ሌሎች ተግባሮች መፈፀም አለባቸው። በአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂው መሰረት ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ማስፋት ያስፈልጋል። ምርትና ምርታማነት ሲሰፉና ሲጎለብቱ የድርቅ አደጋ በሚያጋጥምበት ወቅትም ቢሆን ትርፍ ምርት ለመያዝ ይቻላል። በመሆኑ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተግባሩን መከወን የድርቅ አደጋን ለመከላከል የሚያስችል ይሆናል።

 

ታዬ ከበደ

 

 

 

 

Published in አጀንዳ

 

ኢትዮጵያ በማያቋርጥ የዕድገት ግስጋሴ ላይ ትገኛለች። ይህ ግስጋሴዋ እውን ይሆን ዘንድ ደግሞ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነች ቢሆንም የሚቀሯትና ማሳካት የሚገባት ሥራዎች በርካታ ናቸው፤ እነዚህን እውን ለማድረግም ሁሉም የድርሻውን ማበርከት ይኖርበታል። ከዚህ አንጻርም ባለፉት ዓመታት የተከናወኑትን ስኬታማ ሥራዎችና መልካም ተሞክሮዎች የሚሰፉበት እንዲሁም አገሪቱን አጋጥመዋት የነበሩትን ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ዳግመኛ እንዳይከሰቱ በሚከላከሉ ሁኔታ ላይ በማተኮር የህዝቦች የላቀ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ግልጽና ሰፊ ወይይት በማድረግ ለተግባራዊነቱ በትኩረት መስራት ከኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚጠበቅ ይሆናል።

2010 .ም የመጀመሪያው ሚሊኒየም 10 ዓመታት የተገባደዱበት፤ አዲስ ተስፋ የተሰነቀበት፤ በአገሪቱ ለዘመናት ተንሰራፍቶ የነበረው ድህነት ቀስ በቀስ እየተቀረፈ የመጣበትና ተከታታይና ፈጣን ዕድገት እየተመዘገበ ያለበት ዓመት በመሆኑ በዚህ ዓመት ይህ መልካም ተሞክሮ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ በኩል ምክር ቤቱ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት።

ከፍተኛውን የህዝብ አደራ የተሸከመው ይህ ምክር ቤት የተጀመረውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሀድሶ በማስቀጠል እንዲሁም በአማካይ የተመዘገበውን የሁለት አሀዝ ዕድገት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር በኩል የሚኖረው ሚና የጎላ ከመሆኑ አንጻርም በሚያወጣቸው ህጎችና ደምቦች እንዲሁም በሚያጸድቃቸው የተለያዩ አዋጆች ላይ ትኩረት በማድረግ የተጠናከረ የውይይት ባህልን ማዳበር ይኖርበታል።

አምስተኛው የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን መጀመርን ምክንያት በማድረግ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ፡- « አገሪቱ ከነበረችበት ገናና የስልጣኔ ማማ እየወረደችና እያሽቆለቆለች ቆይታ በሁለተኛው ሚሊኒየም መገባደጃ አካባቢ በውድ ልጆቿ መራር መስዋዕትነት ወደ አዲስ የህዳሴ ጉዞ ከገባች ሩብ ምዕተ ዓመትን አስቆጥራለች። ይህንን የተሀድሶ ጉዞዋንም ማስቀጠል የሚቻለው በተለይም ምክር ቤቱ ጠንካራ ሲሆን ነው፡፡ » ብለዋል።

«አገሪቱ በህዳሴ ጉዞዋ በአማካይ 10 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገትን እያስመዘገበች መምጣቷ በዓለም ፈጣን ዕድገት ካስመዘገቡ አገራት ተርታ የሚያሰልፋት ከመሆኑም በላይ ትልቅ ድል በመሆኑ ይህንን ሁኔታ አስቀጥለን መሄድ ከቻልን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ እንደምንሰለፍ እርግጠኛ መሆን ይቻላል» በማለትም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ይህ እንዲሆንም በህዝብ ትልቅ አደራ የተሰጠው ምክር ቤት የሚያወጣቸው የትኛውም ፖሊሲዎች የአገሪቱን ዕድገት ማዕከል ያደረጉና የህዝቡን ፍላጎት መሰረት የተከተሉ መሆን እንዳለባቸው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ይህ በተግባር ከዋለ በርግጥም የዕድገት ግስጋሴው ምሉዕና የማይቆም ይሆናል።

ክቡር ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው በተለይም በውጭ ንግድ ላይ ያለውን ክፍተት አርሶ አደሩና ባለሀብቱ በጋራ ሊያከናውኑ የሚገባቸውን ድርሻ ከተወጡ አሁን ካለው የምርት ጭማሪ በበለጠ ማግኘት እንደሚቻልና በዘርፉ እንቅፋት የሆነውን የጥራት መጓደል እንዲሁም ማነቆ የሆነውን የአቅርቦት ችግር በማሻሻል ሥራ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አስገንዝበዋል።

እነዚህን ማነቆዎች በመፍታትም የህዳሴውን ጉዞ ማስቀጠል እንደሚገባና በ2009 .ም የተገኘውን 220 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወደ 4 መቶ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማድረስ አበክሮ መስራት እንደሚያስፈልግና ከፍተኛ ዋጋን በሚያስገኙ ሌሎች የሰብል ምርቶች ላይም ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። በመሆኑም ይህንን ለማድረግ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የሚቆጣጠሯቸውን መስሪያ ቤቶች ከኋላ ቀር አሰራር ወደ ዘመናዊ አሰራር እንዲሸጋገሩ በማድረግ፣ ጉድለቶች ሲኖሩም በፍጥነት በማረም የማስተካከል ሥራ መስራት ይኖርባቸዋል።

በፌዴራል ሥርዓታችን ውስጥ ትልቅ ሚናን የሚጫወቱት ሁለቱ ምክር ቤቶቻችን የዓመቱን የሥራ መርሐ ግብራቸውን ዛሬ አንድ ብለው ጀምረዋልና ዘንድሮም እንደወትሮው ቀጣይ የሥራ ትኩረታቸው ለአገሪቱ ዕድገት የሚበጅ፣ ህዳሴዋን የሚያረጋግጥና ወደ ከፍታ ደረጃ የሚያደርሱ ህጎችን ማውጣትና አስፈጻሚ አካላትን መቆጣጠር በማድረግ ለሀገራዊ ህዳሴያችን መረጋገጥ አበክረው የሚሰሩበት ሊሆን ይገባል፡፡

 

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።