Items filtered by date: Wednesday, 11 October 2017

ደቡብ አፍሪካዊው ኢንስትራክተር ዳንኤል ቤኒቴ ባሳለፍነው እሁድ የመራው የጋና ከኡጋንዳ ጨዋታ ከጋና እግር ኳስ ማህበር ለክስ ዳርጎታል፣

 

..2018 በሩሲያ አዘጋጅነት በሚካሄደው ዓለም ዋንጫ ላይ ማለፋቸውን ያረጋገጡ የአፍሪካ አገራት የተሳትፎ ትኬትን በመቁረጥ በደስታ ጮቤን እየረገጡ በሚገኙበት ሰዓት የጋና ብሄራዊ ቡድን ለፊፋ ክስ ማቅረቡ ተሰምቷል።

የሩሲያውን የዓለም ዋንጫ ላይ የማለፍ ዕድል ከነበራቸው አገራት አንዷ የሆነችው ጋና ባሳለፍነው እሁድ ካምፓላ ላይ ኡጋንዳን ገጥማ ነበር። የሁለቱ አገራት ፍልሚያ ያለምንም ግብ መጠናቀቅን ተከትሎ የጋና ብሄራዊ ቡድን ከዓለም ዋንጫ ውጪ ሆናለች። በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳየው የጋና ብሄራዊ ቡድን ከዓለም ዋንጫ የመሰናበታችን ምክንያት ናቸው ሲል የእለቱ የመሃል ዳኛ እና ሁለቱ ረዳት ዳኞቹን ለዓለም አቀፍ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፊፋ ክስ ማቅረቡን ጎል የተባለው የመገናኛ አውታር ዘግቧል።

በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳየው የጋና ብሄራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫን ማለፍ ያልቻልኩት በተሰራብኝ ሸፍጥ ነው ሲሉ ክሳቸውን ለፊፋ ማቅረባቸውን ዘገባው ጽፏል። በኡጋንዳ ማንዴላ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ቅዳሜ ኡጋንዳ ከጋና ያደረጉትን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመሩት ደቡብ አፍሪካዊው የመሃል ዳኛ ዳንኤል ቤኒቴ እና ሁለቱ ረዳቶቻቸው ናቸው።

የጋና እግር ኳስ ማህበር ጨዋታው እንደተጠናቀቀ በዛው በማንዴላ ስታዲየም እንዳለ ቅሬታውን ማስገባቱን ዘገባው ጠቁሞ፤ በእለቱ መሃል ዳኛ እና በሁለቱ ረዳት ዳኞች ላይ ያነጣጠረውን ክስ አቅርቧል። ራፋኤል ዳዋሜናስ በ93 ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ግብ ከጨዋታ ውጪ ናት በሚል የእለቱ ዳኞች ውሳኔ ሰጥተዋል። ይሁንና ራፋኤል ከጨዋታ ውጪ አልነበረም። ሁኔታውንም በዳግም የቴሌቪዥን ምስል ከጨዋታ ውጪ አለመሆኑን አረጋግጠናል የሚል ክስ አቅርበዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የጋናው ተከላካይ ፍራንክ አቺሃምፖን ፔላኒቲ ቦክስ ውስጥ ግልፅ ጥፋት ተፈፅሞበታል። በኡጋንዳ ተከላካይ የተፈፀመውን ጥፋት ዳኛው አይተው እንዳላዩ በማለፍ ፍፁም ቅጣት ምት ከልክለውናል። እነዚህንና በርካታ የዳኝነት በደሎችን በጨዋታው ሲፈፀሙ እንደነበር የጋና አግር ኳስ ማህበር በቅሬታው ላይ አስፍሯል።

የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማህበር ፊፋ የዳኞቹን አቅም በሚገባ መለካትና መፈተሽ እንደሚገባውና ጨዋታውም እንዲደገምልን ሲሉ ቅሬታቸውን አስገብተዋል ሲል ዘገባው አስነብቧል።

የጋና እግር ኳስ ማህበር በተለይ የመሃል ዳኛውን አቅም ይፈተሽልኝ ሲል ያቀረበውን ማስረጃ በዘገባው ይዞ የወጣው ሰንደይ ታይምስ ነው። በመሃል ዳኛው ቤኒቴ እና በረዳት ዳኞቹ ኢልድሪክ አድሌዲ እና ስቲቭ ማሪ ላይ የአቅም ችግር እንዳለ ለፊፋ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

እኚህ ዳኛ በ2017 በጋቦን አዘጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት በግማሽ ፍፃሜ ላይ ጃንዋሪ 28 ቡርኪናፋሶ ከ ቱኒዚያ በተገናኙበት ጨዋታ የነበረውን ጨዋታ መዳኘታቸውን ጠቅሰዋል። በወቅቱም አሰልጣኙ የነበራቸው አቅም ደካማነት በሚገባ እንዳሳዩ አመላክተው አቅርበዋል። በዕለተ እሁድ ካምፓላ ላይ ኡጋንዳ ከ ጋና በተጫወቱት ጨዋታ ላይ ዳኛው ትልልቅ ጨዋታዎችን የመዳኘት አቅም እንደሌላቸው በሚገባ አሳይተዋል የሚል ክስ አቅርበዋል። ለዚህ ተግባር ፍትህ እንፈልጋለን ሲሉ የጋና ብሄራዊ ቡድን በአንበላቸው በኩል በቀረበው ክስ ላይ አስፍረዋል።

የጋና ብሄራዊ ቡድን የፊት መስመር ተጫዋቹ አሳሟጂሃን የመሃል ዳኛው ይህን ዓይነት ትልቅ ጨዋታ የመዳኘት የአቅም ችግር እንዳለባቸው ገልጿል። የቴሌቪዥን ድጋሚ ምስሉ የሚያረጋግጠው ተጫዋቹ ከጨዋታ ውጪ እንዳልሆነ ነው። በካምፓላ ማንዴላ ስታዲየም የጋና ብሄራዊ ቡድን በሚታይ ሁኔታ ከ2018 ዓለም ዋንጫ ውጪ እንዲሆን ተደርጓል ሲልም ተጫዋቹ ብሶቱን ተናግሯል።

 

ዳንኤል ዘነበ

 

 

Published in ስፖርት

ፕሪሚየር ሊጉን ለመቀላቀል ያስቻለውን አሰልጣኝ ያሰናበተው የመቀሌ ከነማ እግር ኳስ ክለብ በምክትል አሰልጣኙ እየተመራ ልምምዱን ቀጥሏል ፣

 

የእግር ኳስ ስፖርት በመቀሌ ከተማ የተወዳጅነት ቁንጮን የያዘ ስፖርት ነው።ይሄንኑ ጥብቅ ቁርኝት ትናንት በነበሩት የከተማዋ ወካይ ክለቦች አሳይቷል። አስመስክሯልም።

ይህንንም የትግራይ ክልል ወኪል በነበሩት የጉናና ትራንስ ኢትዮጵያ የእግር ኳስ ክለቦች የትናንት ገድል መለስ ብሎ መመልከት ይቻላል። ጉናም ሆነ ትራንስ ኢትዮጵያ በፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን ስማቸው ዛሬም ድረስ ይነሳል። በተለይ ጉና የፕሪሚየር ሊጉ የጥሎ ማለፍ ሻምፒዮናነት እስከ አፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ደርሷል።ትራንስ በፕሪሚየር ሊጉ በተደጋጋሚ አዳተኛ ደረጃን በመያዝ ይሄንኑ ጥንካሬያውን አስመስክሯል።

የመቀሌ የእግር ኳስ የውጤታማነት ታሪክ በእነዚህ ሁለት ክለቦች ውጤት ጀርባ ይንፀባረቃል። ከተማዋ ከአገር አልፎ በአፍሪካዊ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ እንደነበረች ያስመሰክራል። ይሄ ጊዜ ምናልባትም ወርቃማው የመቀሌ ከተማ የእግር ኳስ ጊዜ የሚያስብለው ነው። የኳስ አፍቃሪውን የክልሉም ሆነ የትግራይ ከተማ ህዝብ በወከሉት በሁለቱ ክለቦች ውጤታማነት ከድላቸው ጋር የደስታ ጮቤን ሲረግጥ ቆይቷል።

ይሄው ጉዞ ግን ካለፈው አሥር ዓመት ወዲህ ቆሟል። የእነዚህ ጠንካራ ክለቦች የውጤታማነት ጉዞ ተግትቷል። የክለቦች ገናናነት ተደብቋል። ከትራንስ ኢትዮጵያ እና ከጉና ውጤት ጋር አብሮ ጮቤ ሲረግጥ የነበረው የመቀሌ ከተማም ሆነ የትግራይ ህዝብ የእግር ኳስ ስሜት ከክለቦቹ መንሸራተት ጋር አብሮ ወርዷል። የትናንቱን ታሪክ እያሰበ እና እያስታወሰ በቁጭት ዓመታትን ተራምዷል። የመቀሌ ህዝብም ሆነ የክልሉ ነዋሪ የፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ውድድር ናፋቂ ሆኖ ቆይቷል።

ይሄንኑ ቁጭት በ2009 .ም በብሄራዊ ሊግ ተሳታፊ በነበረው የመቀሌ ከነማ አማካኝነት ሰብሮታል። ከብሄራዊ ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ካለፉት ሦስት ክለቦች አንዱ በመሆንም የመቀሌን ወርቃማው የእግር ኳስ ጊዜ ለመመለስ ጉዞው መጀመሩን አብስሯል። በፕሪሚየር ሊጉ ተወካይ ያገኘው የከተማዋ ነዋሪም አንዱን ህልሙን ለማሳካት ችሏል። ቀጣዩ ጉዞውና ምኞቱ የሚሆነው በፕሪሚየር ሊጉም ሆነ በአፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮና ላይ የነበረውን ስምና ዝና መመለስ ነው። በእነ ጉና እና ትራንስ ያጣጣሙትን ውጤት መድገምን ያልማሉ።

የደጋፊውን ስሜትና ምኞት ለማሳካትም ክለቡ ዝግጅቱን ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል። የዝግጅት ክፍላችንም ቀድሞ በዳሽን ቢራ፣ ሃረር፣ በትራንስ ኢትዮጵያ እና በተለያዩ ክለቦች በተጫዋችነት ካሳለፉትና አሁን የመቀሌ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ቡድን መሪ ከሆኑት አቶ ተክላይ እያሱ ጋር በመቀሌ ከነማ እግር ኳስ ክለብ አመሰራረት፣ ቅድመ ውድድር ዝግጅት እና ተጓዳኝ ጉዳዮች ላይ ቆይታ አድርጓል፡፡ በዚህ ቆይታችን ያገኘነውን መረጃ እንዲህ አቅርበነዋል።

ወርቃማ የእግር ኳስ ታሪክ

መቀሌ ከተማ የተለያዩ ስፖርቶች በስፋት የሚዘወተሩባት ከተማ ነች። ከእነዚህ ስፖርቶች ደግሞ የብስክሌት ስፖርት እና እግር ኳስ ክልሉም ሆነ ከተማዋ የሚታወቁበት ነው።በተለይ በእግር ኳሱ የነበረው እንቅስቃሴ በአገር አቀፍ ደረጃም ብቻ ሳይሆን በአህጉር የክለቦች ሻምፒዮና ድረስ የዘለቀ ታሪክ እንዳለ አቶ ተክላይ ያስታውሳሉ።

እርሳቸው ለአሥር ዓመታት በተጫዋችነት ካሳለፉበት የትራንስ ኢትዮጵያ እስከ ጉና የነበረውን ውጤት ለዚሁ ምስክርነት ያቀርባሉ። ጉና የጥሎ ማለፍ ዋንጫን በማንሳት ለመቀሌ ከተማ ነዋሪዎችን ጮቤ ያስረገጠበት የታሪክ አጋጣሚ አለው። በፕሪሚየር ሊጉ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪነቱን በማሳየትም በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ሻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ የቻለ ክለብ ነው። ይሄም የክለቡን የጥንካሬ ደረጃን ለመመስከር የሚያስችል ነው። ሌላው የክልሉ ወካይ ክለብ የሆነው ትራንስ ኢትዮጵያ በፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮና የመሆን ጥግ በተደጋጋሚ የደረሰ ክለብ ነው። ከዚህ ውስጥም በ1996 .ም ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል። በ1997 እና 1999 .ም ባለው ጉዞውም አንዴ ሁለተኛ አንዴ ደግሞ አራተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል። ይሄን የመሰለ ታሪክ ባለቤት ቢሆንም ክለቡ እያሽቆለቆለ በመምጣት በ2003 .ም ሊወርድ ችሏል። የጉናም ሂደት ከዚሁ ተመሳሳይ መንገድ በመያዝ ከፕሪሚየር ሊጉ ወርዷል።

ጉና የነበረውን ውጤትና ዝና ባጣ መልኩ ለበርካታ ዓመታት በሃየር ሊግ እንቅስቃሴውን ማድረግ ጀመረ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የነበረው ጉና እግር ኳስ ክለብ አቅሙ እየተዳከመና ውጤት እየራቀው ሄዷል። የትራንስም መንገድ ከዚሁ ጋር አብሮ የተራመደ ነበር። ትናንት በውጤታማነታቸው ተጠቃሽ የነበሩት የከተማዋ ፍሬዎች ከአሥር ዓመታት በኋላ ለመድረቅ ችለዋል። ውጤታማነታቸውን ከማጣታቸው ባሻገር ለመበተንና ለመፍረስ የሚንገዳገዱ ክለቦች ሆነዋል።

ታሪክን ለመድገም የተመሰረተው መቀሌ ከነማ

በሃየር ሊግ የሚጫወተውን ጉና ዕጣ ፈንታ በመመልከት ከተማ አስተዳደሩ እና የስፖርት ኮሚሽኑ አስተዳደሮች ከአንድ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን አቶ ተክሌ ያስታውሳሉ። የጉናን የመፍረስ ስጋት በማስወገድ እንደ አዲስ ማጠናከር ከሚል መግባባት ላይ በመድረስ ተግባሩ ሊጀመር ቻለ። ይሄውም የሆነው በ2002 .ም ጉና በሃየር ሊጉ ተሳትፎ እያደረገ ባለበት ወቅት ነበር። ከዚህም ጀምሮ መቀሌ ከነማ የሚለውን ስያሜ ይዞ እንደ አዲስ ጉዞውን ጀምሯል።

ክለቡንም በተጫዋቾች፣ በፋይናንስ እንዲሁም በማኔጅመንት በኩል ትኩረት በመስጠት እንደ አዲስ ተዋቀረ። መቀሌ ከነማ እግር ኳስ ክለብ የሚል ስያሜን በመያዝ ጉዞውን ሊጀምር ችሏል። የከተማዋን የትናንት እግር ኳስ ውጤትና የህዝቡን የእግር ኳስ ፍቅር መሰረት በማድረግም አስተዳደሩ ጉናን በመረከብ እንደ አዲስ መንቀሳቀስ ከጀመረ ስምንት ያህል ዓመታት አልፈዋል። ክለቡ ይሄንኑ ጉዞ ሲጀምር አንድ አላማ ያደረገው የህዝቡን ቁጭት በማስረሳት፣ ያለፈውን የጉናን እና ትራንስን የውጤታማነት ዘመን መድገም ነው። በፕሪሚየር ሊግ ተሳትፎን፣ ተፎካካሪነትን፣ ውጤታ ማነትን ለማሳካትም የአምስት ዓመታት ጉዞ አድርገዋል። መቀሌ ከነማ የሚለውን ስያሜ ይዞ ከገባ ጀምሮም በሃየር ሊጉ ላይ የነበረው ውጤት ተቀይሯል።ቀድሞ የነበረው የጉናን ደካማ ጉዞን በማደስም ጠንካራ ክለብ በመፍጠር ወደ ብሄራዊ ሊግ ለማለፍ ተችሏል።

2005 .ም በብሄራዊ ሊጉ የነበረው ተሳትፎም የክለቡን እየተጠናከረ መሄድን የሚያሳይ እንደነበር በቡድን መሪው በኩል ይነሳል። በ2005 .ም የተሳትፎውን ደረጃ ከፍ ማድረግ ችሏል። በውድድሩ ላይ መልካም የሚባል ደረጃን በመያዝ ወደ ብሄራዊ ሊግ ላይ ማለፍ ችሏል። የሱፐር ሊጉ ቆይታውም፤ ሃየር ሊጉ ላይ የነበረውን ጥንካሬ ደግሞ አሳይቷል። በተለይም በ20062007 እና 2008 .ም ላይ የነበረው እንቅስቃሴ ለዚሁ ማሳያ ተደርጎ በአቶ ተክላይ የሚጠቀስ ነው።

ክለቡ በ2006 .ም ድሬዳዋ ላይ ወደ ለፕሪሚየር ሊግ ለማለፍ በተደረገው ውድድር ተሳትፏል። ምንም እንኳን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማለፍ ባይቻልም መልካም ተሞክሮ በመያዝ ተመልሷል። ድሬዳዋ ላይ እንደነበረው እንቅስቃሴ ሁሉ በሁለቱ ዓመታት ብሄራዊ ሊግ ላይ ጥሩ ተፎካካሪ የሆነ ክለብ ነው። በ2008 .ም በብሄራዊ ሊጉ የውድድር ዘመን ላይ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ማሳየት ችሏል። የእንቅስቃሴው ደረጃ ግን ከፕሪሚየር ሊጉ ለማለፍ አላስቻለውም ነበር። የጥረታቸውን መጠን በማሳደግም በ2009 የውድድር ዓመት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መቀላቀል ችሏል። ቀጣዩ ጉዞ የሚሆነው ከተማዋን ይወክሉ የነበሩትን የእነትራንስና ጉና የነበራቸውን ውጤታማነት፣ የፕሪሚየር ሊጉ ተፅዕኖ ፈጣሪነትን ዳግም መጨበጥ እንደሆነ አቶ ተክላይ ይናገራሉ።

የብሄራዊ ሊጉ ፈተና እና ድል

2009 ውድድር ዓመት መቀሌ ከነማ ፕሪሚየር ሊጉን ለመቀላቀል የበለጠ ራሱን አዘጋጅቶ የገባበት ወቅት ነው። ጠንካራ ዝግጅት አድርጎም ውድድሩ ላይ ተገኝቷል። ይሄንኑ ሁኔታም በብሄራዊ ሊጉ የመጀመሪያው ዙር የውድድር ምዕራፍ አንደኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቆ አስመስክሯል። ይሁንና በውድድሩ ሁለተኛ ዙር ላይ በመጣበት ሁኔታ አልተጓዘም። የጨዋታዎች መደራረብና ጫና እንዲሁም፤ ሁሉም ክለቦች ለማለፍ የሚያደርጉት ጠንካራ ፉክክር ከባድ ጊዜ እንዲሆንበት አድርጓል።

ጫናዎቹን በመቋቋምም እስከ መጨረሻውና መሄድ እስከሚችልበት ደረጃ ተጉዟል። ከብሄራዊ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚቀላቀሉት ሦስት ክለቦች እንደሆነ ይታወቃል። እነዚህን ለመለየት ደግሞ አንዱ የብሄራዊ ሊጉ ውድድር ሲሆን፤ የጥሎ ማለፍ ውድድር ላይ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

ቀጣይ ምዕራፍ

2010 .ም መቀሌ ከተማ በስሟ በሰየመችው ክለቧ በፕሪሚየር ሊጉ ላይ የሚወክላት ክለብ ማግኘት ችላለች። ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መግባት የሚለውን የመጀመሪያውን ምዕራፍም ማሳካት አስችሏል። ቀጣዩ ጉዞ የሚሆነው በፕሪሚየር ሊጉ ላይም ሆነ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና ላይ ካለው የታሪክ ምዕራፍ መድረስ ነው። ይኸውም ቀጣይ ጉዞ ይሆናል ማለት ነው። አሁን ያለው የመቀሌ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ቀድሞ የነበረውን የጉና እና የትራንስን ውጤታማነት የመድገም ህልሙን በማንገብ ጉዞውን ጀምሯል።

ቀጣዩ ፈተና እና ዝግጅት

የክለቡ ጉዞ አንዱ አካል ለሆነው ለ2010 .ም የፕሪሚየር ሊጉ ተሳትፎም ዝግጅቱን በተጠናከረ ሁኔታ ማድረግ መቀጠሉን አቶ ተክላይ ይናገራሉ። መቀሌ ከነማ በሁለቱ ውድድሮች ማለትም በሃየር እና ሱፐር ሊግ ያጋጠሙትን ፈተናዎች በማለፍ ዛሬ ላይ ደርሷል።አሁን ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ ለሚኖረው ውድድርና የሚያጋጥመውን ፈተና ለማለፍ ዝግጅት እየተደረገ ነው። ይሄንኑም ተግባር ባለፈው ዓመት ነሐሴ አንድ ቀን ነው የጀመረው። አዲስ ያስፈረማቸውን እና ነባር የክለቡን ተጫዋቾች ማሰባሰብ ልምምድ በማድረግ ላይ ይገኛል።

አቶ ተክላይ እንደሚሉት፤ በፕሪሚየር ሊጉ ልምድ አለመኖር እንደ አንድ ፈተና የሚጠቀስ ነው። ክለቡም ይሄንን መሰረት አድርጎ ነው የተዘጋጀው። በፕሪሚየር ሊጉ ላይ የሚጫወቱ ተጫዋቾችንና ፕሮፌሽናል ተጫዋቾችን አስፈርሟል። ሁለት ያህል ፕሮፌሽናል፣ ወደ 20 የሚሆኑት ደግሞ ከተለያዩ የአገሪቷ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች አዘዋውሯል። ይሄን ማድረጋቸውም የልምድ ችግር የሚለውን የመጀመሪያውን ስጋት ለመቅረፍ ያስችላል የሚል እምነት አላቸው።

2010 .ም የክለቡ ህልም

የዘንድሮው የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ተሳትፏቸው እንደመሆኑ በፕሪሚየር ሊጉ መቆየት የሚል እቅድ ትልቁ ትኩረታቸው እንደሆነ ነው የቡድን መሪው የሚናገሩት። በፕሪሚየር ሊጉ ላይ መቆየቱን ማረጋገጥ ሲችል ደግሞ ቀጣይ የሚኖረው እቅድ የትናንቶቹን የከተማዋን ወካይ ክለቦች ፈለግ የተከተለ ሥራ መስራት ይሆናል። እንደ ትራንስ እና ጉና የፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ክለብ መሆን። ደረጃ ሰንጠረዙ ውስጥ በመግባት ሻምፒዮና መሆን። አለፍ ሲል ደግሞ እንደ ጉና እግር ኳስ ክለብ በአፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮና ላይ ተሳትፎ ማድረግ የሚሉ ህልሞች እንዳሉት የቡድን መሪው ተናግረዋል።

12 ኛው ተጫዋች ጉዳይ

በፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የነበሩት ጉናና ትራንስ ኢትዮጵያ በመውረዳቸው ምክንያት ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት የስፖርት ቤተሰቡና ደጋፊው ሞራል ተዳክሞ መቆየቱን አቶ ተክሌ ይገልፃሉ። ዳግም ተመሳሳይ ዕድል እንዳይገጥማቸው ደጋፊው አቅሙ በፈቀደው ሁሉ ክለቡን ይደግፋል።ያበረታታል። ለክለቡ የተጠናከረ ድጋፍ ሲባል የደጋፊዎች ማህበር እንደ አዲስ የማወቀር ተግባር እየተሰራ ነው። ይሄ መሆኑ ክለቡ ጠንካራና የተጠናከረ ደጋፊ እንዲኖረው ያደርጋል። ከዚህ ባሻገር ደግሞ ደጋፊው ስፖርታዊ ጨዋነትን በተላበሰ ሁኔታ ድጋፉን እንዲሰጥ የሚያስችል ነው። በመሆኑም ክለቡ ዛሬ ላይ ለመድረስ የደጋፊው ሚና ከፍተኛ እንደነበረው ሁሉ ለነገም ጉዞው የሰመረ መሆን ይሄንኑ ሚናውን በጨዋነት አብሮ የሚሄድ ይሆናል ሲሉ ነው አቶ ተክሌ አስተያየታቸውን የቋጩት።

 

ዳንኤል ዘነበ

 

Published in ስፖርት
Wednesday, 11 October 2017 18:01

ደብዳቤው 2

ይድረስ ለተከበርከውና ለታፈርከው ወዳጄ አያ! ሻረው

እነሆ ! አዲሱን አመት ከህዝቤ እኩል በኮሽታ ማነው? እ…በከፍታ እጀምረዋለሁ ስል በኩምታ ተቀበልኩት፡፡ «ምነያታልኸኝ ደግሞ ይኸውልህ በክረምት ብርዱንና ዝናቡን ችየ የጉልበት ሥራ እየሠራሁ አልበላም፣ አልጠጣም ብየ ካጠራቀምኩት ገንዘብ ላይ ሁለት ሺ ብሬን ላጥ አርጌ ቡጭ ቡጭ የሚለውን ስልክ ገዛሁልህ፡፡ ተያ በኋላ አንድ አምስት ቀናት ያህል ቡጭ ቡጭ እያረግሁ አከራዬን እማማ ሽብሬን ሳሽኮረምምበት ሰነበትኩ፡፡ እሳቸው ግን አንድ የህንድ ወጣት ኩሽና ለኩሽና ከሴት ጋር ሲልከሰከስበት የሚውል ፍልም ላይ ማፍጠጥ ጀምረው ኖሮ እኔን ከናካቴው እረሱኝ፡፡

ታዲያ በአንድ የተረገመ ማክሰኞ ምሽት በሰፈራችን ከታወቀ ጠጅ ቤት ጎራ አልሁልህ። ከጠጅቤቱ አንድ ስንቄ የሚሏት መልከ መልካም ኮማሪ ቅም ብላኛለች ።እናልህ አንድ ሁለት እያልኩ እሷን ላሽባባ አስቢያለሁ፡፡ ዛዲያ በቤቱ አዋቂው ብትል ውርጋጡ ባለ ቡጭ ቡጭ ነው፡፡ ሁሉም ሙባይሉን ቡጭ ቡጭ እያረገ ዳንኪራ ላክልኝ፣ ፉከራ እየተባባለ ዘፈንና አሸሸ ገዳሚውን ይላላካል፡፡

እኔም ያች ስንቄ …አይ ስንቄ ምን አለ አንዳች መብረቅ በሰለቃት… ከሰው እኩል መሆኔን ላሳያት ብዬ ስልኬን መዥልጨ ሳበቃ... ኤዲያ! ለካስ የኔው ሙባይል ከቡጭ ቡጭ በተቀር እንደሌላው ውርጋጥ አሸሸ ገዳሜ የለበትም ኖሯል፡፡

እሷ ግና ስልኩን ስታይ ያን ፍልቅልቅ ጥርሷን እያሳየችኝና ብርሌየን እየሞላች «እስኪ ሙዚቃ አሰማኝ» አለችኝ፡፡ አኔም «ለግዜው የለውም» ስል ፈጥኜ መለስኩላት፡፡ ለጥቃም «ለምን ከሰው አትቀበልበትም» ብትለኝ ሀሳቡ ደግ መስሎኝ አንዱን ላክልኝ አልኩትና ቡጭ ቡጭ ማድረግ ጀመርሁ። ለካንስ መቀበሉም፣ መላኩም የራሱ ብልሀት ኖሮታል፡፡

እኔ ብልሀቱ መች ገብቶኝ? ለካንስ ልጁ ሲደናገረኝ አይቶ «አክፍልኬሽን» ነው ምንትስ ብቻ እንጃለት መጀመሪያ እሱ መላክ አለበት አለኝና ሰጠሁት፡፡ ትንሽ ጎራጉሮት ሲያበቃም ከኔ ስልክ ጋር ስላልተገናኘ በእገሌ ስልክ ይሞከር ብሎ ለሌላኛው አቀበለው፡፡ ያኛውም ለሌላኛው፡፡ ያም ነካካና «ስልኩ ግን ያበደ ስልክ ነው» እያለ ለወዲያኛው...

እኔም የሰው አልበቃ ብሎ ስልክ ሳይቀር የሚያብድበት የጉድ አገር እያልኩ አይኔን ከሙባይሌ ሳልነቅል እከታተላለሁ፡፡ ጠጁንም መጎንጨቴን አልረሳሁም፡፡

ድንገት ያች ስንቄ… አንዳች እንቅ አርጎ ባስቀራት … ደርሳ ብርሌየን ሞላችና ካጠገቤ ተቀመጠች። እኔም ከሷ ጋር ወሬየን እሰልቅልህ ገባሁ፡፡ እንዲያም ሲል ጠጁን ስደጋግም፣ ስንቄዋም ለሌላው ቀድታ ወደኔ ስትመላለስ ቆየች። በኋላም ብርሌየን ሞልታ ከጎኔ አንድያዋን ቁጭ አለችልኝ። እንደለመደችው በዚያ ፍልቅልቅ ሳቋ ልቤን ታጠፋው ብትይዝ ደግሞ ስልኩ ከነመኖሩም ረሳሁት፡፡

አዲሱ ሙባይሌን ምድረ- ወሮ በላ ተቀባብሎት ሲያበቃ «ባትሪ ጨርሷል ነገ ሞልተህ ስታመጣው ሙዚቃውን እንልክልሀለን» ብለው መለሱልኝና እንደ ጅብ እየተጠራሩ ጠጁን ቤት ጥለው ውልቅ አሉ፡፡ እኔም ነገሩን ከጤፍ ሳልቆጥር ሙባይሉን ወደ ኪሴ አስገባሁ።

ከስንቄ ጋር ብቻችንን ስለቀረን ደስ በሎኛል። ከእሷ ዘንድ እንዲያ እንዲያ ስል ቆየሁ። ጥቂት አምሽቼም ወደ ቤቴ አመራሁ፡፡ ጠዋት ነቅቸ ስልኩን ላስነሳ ከኮረንቲው ጋር ሰካሁት። እሱ እቴ ብለው ብሰራው ወይ ፍንክች! ብልጭ እንኳን አላለም። ጠላትህን ግራ ይግባውና ግራ ገባኝ። ትንሽ ቆይቸ ሳስተውል ግን የያዝኩት ስልክ ቀለሙና መጠኑ የኔን ይምሰል እንጅ የተጫጫረና ጀርባው የተሰነጠቀ ነው። በደንብ ሳስተውለውም ሰካራም የቆመበት ጣሳ ይመስላል፡፡ ደነገጥሁ። ወዲያው ሆድና ጀርባውን ብከፍተውስ ጠጠር የተጠቀጠቀበት ባዶ ማይካ...

በቁጣ እየፎከርኩና እየፎገላሁ ወደዚያው ጠጅ ቤት ኸጀ ስንቄን ጉሩምቦዋን አንቄ እነዚያን ወሮ በሎች ውለጅ እያልኩ ግስላ ሆንኩ። ኤዲያ! ምን ዋጋ አለው ብለህ? ጥቂት እንኳን ሳይቆይ ባካባቢው የነበሩ ደረሱ። «እንዴት ሴት ልጅ ላይ እጅህን ታነሳለህ» እያሉም በነገር አካለቡኝ ፡፡

ግር ግሩን ሳስበው ለካንስ የሰርጌ እለትም እንደዚያ ቀን አልደመቀልኝ ኖሯል ፡፡ አይ ስንቄ! አይ ስንቄ! …ማታ አለሜን አሳይታ ጠዋት አለሜን ወደ ኩምታ አጠንጥናልኝ አረፈችው፡፡ ደግሞስ የተዘረፍኩት ሳያንስ ሴት ላይ ጥቃት ፈጥሟል ተብየ በፖሊስ መያዜ ? ጣቢያ ገብቼ ታሰርኩልህ እኮ! አዲሱንም አመት እዚያው ታጉሬ በኩምታ አከበርኩት እልሀለሁ ፡፡

ዘር ይውጣላቸውና እማማ ሽብሬ ናቸው ሰልስትና ዋስ ሆነው ያስፈቱኝ፡፡

አይ…አይ! የኔ ነገር ሞት ይርሳኝና የእናታችሁን ሞት ሰምቸ እጅጉን ማዘኔን ሳልነግርህ አያ! ሻረው ወዳጄ የራሴን እሮሮ ብቻ አዘነብኩብህ፡፡ በእውነቱ ሞት ለሁላችንም ነውና በርታ በርታ በሉ፡፡ ብዙ ማዘን ደግም አይደል፡፡ እስቲ አይዟችሁ፡፡

ያው እኔም ከብኩንነት አትውጣ ተብሎ የተጻፈልኝ ይመስል እንደ አውሎ ነፋስ ከዚያ ከዚህ የሚንጠኝ ነገር አላጣም፡፡ እማማ ሽብሬ ካስፈቱኝ በኋላ እሳቸውም እዚያ ቅንቅናም ተለቢዥናቸው ላይ እንዳፈጠጡ ነው። ደህና ቀንቶኝ እኔም ማየት ስጀምር አንዲት ስሟ የጠፋባት ወጣት ሴትዮ ስለተፈጥሮ አደጋ እናውራ ብላ የቤቱ አባወራ ሆና ቁጭ፡፡

ለነገሩ ሲያዩዋት ሸጋ ቢጤ ናት። እስኪ ጉዷን ልይ ብዬ ተብሊዥኑ ላይ ባፈጥ ምንትስ የሚባለው አውሎ ነፋስ በእንትን አገር የዛሬ ምንትስ አመት ያደረሰው አደጋ ይህን ያህል ሰው ገድሎ ይህን ያህል ዶላሬ ኪሳራ አደረሰ ትላለች፡፡ በደምብ ሳስተውላት ከሰው ህይዎት ይልቅ ያከሰረውን ዶራሬና አመተ ምህረቱን ትጠቁማለች። አደጋው ውስጥ ተቀምጠው ወሬ የሚያቀብሉ ጋዜጥኛዎችን ወሬ በተብሊዥን ለማስተላለፍ ከነፋሱ ጋር ሲውተረተሩም እያሳየች ነው።

ወሬ እንደሁ ከነፋስ ይፈጥናል፡፡ መቼም እስካሁን «የጋዜጠኛ ያለሽ» የሚያሰኝ ጉዳይ ተፈጥሮ አይቸ አላውቅም፡፡ ግን በተብሊዝን ያለችው ሴት ብብት ማሽተት ስራ ነው ብላ በህዝብ ፊት መናገሯ ምን ይሉት ዘመናዊነት ነው?

አበስኩ ገበርኩ፡፡ አዬዬ...አምና የሰው እዳሪ መድፋት፣ ዘንድሮ ደግሞ የሰው ብብት ማሽተት እንጀራየ እንዳይሆን ብቻ ? ይህንኑ እያሰብኩ ከራሴ ጋር ስከራከር አንዱ ድንገት «ስማ! ቆምጬ ስራ ተገኝቶላሀል እሳቸው ለግቢያቸው አትክልት ኮትኳች ይፈልጋሉ» አለኝ ፡፡

«ቆምጨ» ስላለኝ ነዶኛል። እኔም ከአዲስአቤዎች ለጆሮዬ የጠገብሁትን ስድብ «እናትህ ምንትስ»… ልለው አሰብኩ። ግን ሌሎች የሚሉትን መድገም ነውር መሆኑ ገባኝና ከአፌ መልሼ ስራውን በምስጋና ተቀበልሁ፡፡ ወዳጄ! አያ ሻረው ዛዲያ አዲሱ ስራየ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? አይይይይ... ባልነግርህ ይሻላል፡፡ ሌላ ግዜ በሰፊው አጫውትኃለሁ፡፡

ያንተው! ወዳጅህ አፌ ማር

ተአዲስአባ

 

ሄኖክ ጥበቡ

 

Published in መዝናኛ
Wednesday, 11 October 2017 17:54

አርሂቡ…ኑ ቡና ጠጡ

 

ኢትዮጵያ የቡና መገኛ አገር ብቻም ሳትሆን የቡና ወዳጅ አገር ናት ቢባል ቅጥፈት አይሆንም።ለዚህም ይመስላል በመዲናይቷም ሆነ በሌሎች የአገሪቷ ክፍል የጀበና ቡና ጠጡ ቤቶች በርክተው መታየታቸው። የቡና ጠጡ ስራም ከትላልቅ ሆቴሎች እስከ መንገድ ዳር እስከሚገኙ ደሳሳ ቤቶች ድረስ የሚታይ ትዕይንት ሆኗል። በዚህም በርካቶች ኑሯቸውን የመደጎሚያ አንድ የስራ መስክ አድረገውታል። የአዲስ ዘመኗ መልካም ስራ አፈወርቅም በቡና ጠጡ ስራ በመሰማራት ኑሯቸውን እየገፉ የሚገኙ ሰዎችን በማነጋገር የህይወት ተሞክሯቸውን እንዲህ አቅርበዋለች።

 

ግርግር ከበዛበት ጎዳና ከአንዱ ጥግ ተቀምጣ ወጪ ወራጁን በአትኩሮት ትቃኛለች። በየማህሉ አቧራ እያስነሳ አካባቢውን የሚረብሸው ንፋስም እምብዛም እንዳላወካት ያስታውቃል። የፀሐዩን ግለት የለመደችው ይመስላል። እንደነገሩ በላስቲክ የተቀየሰችው ጠባብ ጎጆ ያልያዘችው የለም። በጎጆዋ ውስጥ እዚህም እዚያም ቋጠሮዎች ይታያሉ። አንባሻ፣ ትኩስ ፓስቲ፣ ጥራጥሬ… ሌሎች ነገሮችን ይዘዋል።

መሀል ለመሀል የተዘረጋው አግዳሚ ጠረጴዛ ላይ የሻይ ብርጭቆዎች ተደርድሮ በእግሮቹ ስር ፔርሙሶችንና ማንቆርቆሪዎችን አዳብሏል። የሚነፍሰው ንፋስ አሁንም አሁንም የመንገዱን አቧራ እያፈሰ ወደ ቤት ያስገባል። ይህ ሁሉ ሲሆን በወይዘሮዋ ፊት ላይ የተለየ ገጽታ አይነበብም። የፈዘዙ አይኖችዋ ወደ ውጭ ማየታቸውን እንደቀጠሉ ነው።

ድንገት ከወደውጭ «ቤቶች» የሚል ድምጽ ተሰማ። በርከት ያሉ ሰዎች ናቸው። ጎንበስ እያሉም ወደውስጥ ዘለቁ። ቤቱን አስቀድመው የሚያውቁት ይመስላል። ይሄኔ በትካዜ ቆዝማ የነበረችው ሴት በፍጥነት ከመቀመጫዋ ተነሳች። እንግዶችዋን ቦታ አስይዛም በረከቦት የተደረደሩ ሲኒዎችን መልክ ማስያዝ ጀመረች። ዝምታ ውጦት የነበረው ስፍራ በእንግዶቹ ጨዋታ ደመቀ። የተዳፈነ የሚመስለው ከሰል ተያይዞ ቤቱ በእጣን ሽታ ታወደ። ትካዜ የለበሰው የወይዘሮዋ ገጽታ በአንዴ በደስታ ሲፈካ ታየ።

ዕድሜ ጠገቡ የቡና እረከቦት መልከ ብዙ ስኒዎችን አጠጋግቶ ደርድሯል። ቀድሞ ቡና የተቀዳበቸው ስኒዎች መድረቅ የጀመረው ጭላጭ አተላ በሴትዬዋ ሸካራ እጆች ተለቃልቀው ለሥራ ተዘጋጁ። ባለቡናዋ ደስ እንዳላት ያስታውቃል። ወይዘሮ ዘሪቱ አረቦ በዙሪያዋ ከበው የእሷን እጅ የሚጠብቁ ደንበኞችዋን በወጉ ለማስተናገድ ሽር ጉድ እያለች ነው።

ከተስተናጋጆቹ አብዛኞቹ በአካባቢው የቀን ሥራ ላይ የሚውሉ የጉልበት ሠራተኞች ናቸው። ብዙ ጊዜ የምሳ ቋጠሯቸውን ፈተው እህል ውሃን የሚቃመሱት በእሷ ጎጆ ነው። ይህ ባይሆን እንኳን አንባሻና ፓስቲ በልተው ትኩስ ቡናዋን ፉት ለማለት ከስፍራው አይታጡም። ቡና መኖሩን የሚያውቁ አንዳንድ መንገደኞችም አምሮታቸውን ለመወጣት ከጎጆዋ ጎራ ማለታቸው ተለምዷል። በአካባቢው በጉልት ንግድ ላይ የሚውሉ ሴቶችም የዘሪቱ የዘወትር ደንበኞች ናቸው። ለአንድ ስኒ ቡና አራት ብር እየከፈሉ በተወዳጁ ቡናዋ ይስተናገዳሉ።

ወይዘሮ ዘሪቱ አረቦ ሦስት ልጆችዋን ያለ አባት ስታሳድግ ብርታት ተለይቷት አያውቅም። ባለቤቷን በሞት ካጣች ወዲህ ልጆችዋን የማስተዳደር ኃላፊነት በትከሻዋ መውደቁ ግድ ነበር። ኑሮን ለማሸነፍ ያልሞከረችው የለም። እንጨትና ቅጠል ለቅማ ሸጣለች። በየሰው ቤት እየዞረችም ጉልበቷ የሚፈቅደውን ሁሉ ሰርታለች። ሁሌም ከፊቷ የማይለየው ደማቅ ፈገግታ ጨዋታዋን በሳቅ እያጀበ ከብዙዎች ጋር ያግባባታል።

"የእኔ" የምትለው ቤት የላትም። ለእሷ ዘመዷ ጉልበቷ ነውና ሌት ተቀን ብትለፋና ብትሮጥ ደከመኝን አታውቅም። የሚረዳትና አይዞሽ በሚላት ወዳጅ ዘመድ ላይም መመካት አትችልም። እሷ ሁሌም ቢሆን በልጆችዋ ላይ ተስፋ እንደጣለች ነው። አንድ ቀን ለቁምነገር ደርሰው፤ ለወግ ማዕረግ እንደሚበቁ ስታስብ ውስጧ ሀሴት ይሞላል። ከጥቂት ጊዚያት ወዲህ በአዕምሮ ህመም ሳቢያ ቤት መዋል የጀመረችው ሴት ልጇ ጤንነት ሁሌም ያሳስባታል። "አደራ" ብላ የምትሰጠው የቅርብ ሰው የላትም። እሷን ከቤት ትታ ሥራ ስትሄድ ልቧ በሥጋት እንደተሞላ ይውላል። ከዚህ ጭንቀት ለመዳን ያላት አማራጭ ከመንደር ቤቶች ይልቅ ኮንደሚኒየም መከራየት ነበር። ይህን ስትወስን ግን ክፍያውና የዕለት ገቢዋ አልጣጣም ብሎ ፈትኗታል። በየቀኑ ቡና እያፈላች የምታገኘውን ለኪራይ ስትከፍል ለጓዳዋና ለቀለብ እጅ እያጠራት በሀሳብ የምትብሰለሰልበት ጊዜ የበዛ ነው።

ሳቂታዋና ተጫዋችዋ ዘሪቱ ግን ሁሌም በፈገግታ ተሞልታ የነገን መልካም ተስፋ በጉጉት ትጠብቃለች። የጀበና ቡናዋን ከዘወትር ደንበኞችዋ ጋር ያኑርላት እንጂ በኑሮዋ መቼውንም ቢሆን አትከፋም። ሁሌም ከእሷ ይልቅ የተሻለ ስፍራን መርጠው የሚሄዱ ቡና ወዳዶች እንዳሉ ታውቃለች። ገበያ ዕድል ነው ብላ የምታምነው ወይዘሮ ግን በዚህ ሆድ ብሷት አያውቅም። አልፈው የሚሄዱትን በአይኖችዋ ሸኝታ ወደእሷ የሚመጡት «አርሂቡ»ለማለት ሁሌም ዝግጁ ነች።

ዘሪቱን ተሰናብቼ ከቤቷ ወጣሁና መደዳውን የጀበና ቡና ያለባቸውን ቤቶች በወፍ በረር መቃኘት ጀመርኩ። አብዛኞቹ የተሻለ እይታን ለመሳብ የሚወዳደሩ ይመስላሉ። የቡና አፈላልን የሚያሳዩ በርካታ ስዕሎችን ጨምሮ ባህላዊ መጋረጃና አልባሳቱ፣ መቀመጫውና የስኒ መደርደሪያው አንዱ ከሌላው ለመላቅ የተዘጋጁ መሆናቸውን መገመት ይቻላል። በጀበና ቡናው አካባቢ ያሉ ደንበኞች ተግባረ ብዙ ናቸው። በእጃቸው ጫት የያዙትን ጨምሮ ለጨዋታ የሚገናኙት ሁሉ በዕጣኑ መአዛ እየታወዱ የልብ የልባቸውን ያወጋሉ።

መልከ ብዙዎቹን የጀበና ቡና አካባቢዎች አልፌ ከአንድ ዘመናዊ ህንፃ ውስጥ ተገኝቻለሁ። ይህ ህንፃ ከከተማዋ መሀል የሚገኝ ሰፊ የንግድ ማዕከል ነው። የመጀመሪያው ፎቅ ላይ ስደርስ በርከት ያሉ ሰዎች በኮሪደሩ ላይ ከሚገኝና የጀበና ቡና ከሚፈላበት ስፍራ ተሰባስበው ተመለከትኩ። በተመሳሳይ ሁኔታ ሁለተኛው ፎቅ ላይ ስደርስም የገጠመኝ ይሄው ነበር። አሁን በሦስተኛው ፎቅ ላይ ላይ ነኝ ።

በዚህ ቦታ ላይ ደግሞ ቀድሞ ካየኋቸው ቡና ጠጪዎች በቁጥር የላቁ ሰዎች ተሰባስበው የቡናውን መድረስ ሲጠባበቁ አስተዋልኩ። ለቡና ቁርስ የተዘጋጀው ፈንዲሻ ለእንግዶቹ እየታደለ ነው። በመልካም መአዛ የታወደው ስፍራ በደንበኞቹ ሞቅ ያለ ጨዋታ ታጅቦ ቀጥሏል። የቀደሙት ቦታ ሲለቁ አዲስ የሚገቡት ደግሞ በስፍራቸው ይተካሉ።

በዚህ መሀል እንግዶቹን በደማቅ ፈገግታ እየተቀበለ በትህትና የሚያስተናግደውን ወጣት አስተዋልኩ። በህንፃው ላይ የጀበና ቡናን ከጀመሩት መሀል አንዱ ነው። ይህን ወጣት ብዙዎቹ በሬዲዮ የስፖርት ጋዜጠኝነቱ ያውቁታል። ከስምንት ዓመታት ላላነሰ ጊዜም የስፖርት አፍቃሪ አድማጮቹ በሚያቀርበው ዘገባ ጆሯቸውን ሲሰጡት ቆይተዋል።ጋዜጠኛ ዘርአይ እያሱን።

ጋዜጠኛው ኢትዮጵያ ሬዲዮን ጨምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲሠራ ቆይቷል። የእሱ የሙያ ድር የተወጠነው በደቡብ ክልል ሬዲዮና ቴሌቪዢን ድርጅት ቢሆንም የሬዲዮ ፋና የስፖርት ጋዜጠኝነቱ ደግሞ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በእግር ኳስ ላይ ተመርኩዞ የፃፈው «ከሜዳ ውጭ የተሰኘው መጽሐፉም ተነባቢነትን አትርፎለታል። እነዚህን የሙያ አመታት በፍቅር ያሳለፈው ጋዜጠኛ ዘርአይ በውስጡ ሲብሰለሰልበት የቆየውን ዕቅድ ለመፈፀም ጊዜው ስለመድረሱ ያወቀው አንድ ቀን ነበር።

ዘርአይ በቆየባቸው የጋዜጠኝነት አመታት በሙያው ደስተኛ ነበር። ይሁን እንጂ እሱን ጨምሮ አብዛኞቹ በሚያበረክቱት ልክ የሚሰጣቸው ክፍያ በቂ ያለመሆኑን ያምናል። ይህ መሆኑ ደግሞ ኑሮን አሸንፎ ለመቀጠል ያለውን ህይወት አዳጋች ሲያደርገው አስተውሏል። አንዳንዴ ለተጨማሪ ጥቅማ ጥቅም ሲባል የሚፈጸሙ ህገወጥ ድርጊቶች ደግሞ እሱ አበክሮ የሚፀየፋቸው ናቸው። የሙያው ስነ ምግባር ከሚፈቅደው ውጭ ባልተገባ ምግባር የሚሳተፉ አጋሮቹንም ልማድ ያውቀል። ስለዚህ ዘርአይ እራሱን በተሻለ አቅም ለማጠናከር መንገዱን መቀየር እንዳለበት አመነ።

ምንም እንኳን እጅግ ከሚወደው የጋዜጠኝነት ሙያ ለመለየት ፈታኝ ቢሆንበትም ፍፁም መቁረጥ ነበረበት። እናም ለአመታት ከራሱ ሲመክርበት ለቆየው የንግድ ሥራ የቱ እንደሚሻለው ሲያማርጥ ቆየ። በመጨረሻ በውስጡ ሲብሰለሰልበት ለኖረው ዕቅድ ሀሳብ ነድፎ ከውሳኔ ደረሰ። ውሳኔውም ከጀበና ቡና ንግድ ላይ አሳረፈው።

አሁን ዘርአይ ሙሉ ጊዜውን ለጀበና ቡና ንግድ ሰጥቷል። ሥራውን ሲጀምረው በጥቂት የገንዘብ መነሻ ነበር። የሙያ ለውጥ ሲያደርግም ቀላል የማይባሉ ፈተናዎችን ተጋፍጧል። በሥራው ሂደት ኪሣራ ቢያጋጥምና እንደታሰበው ሆኖ ባይገኝ የሚመጣውን ሁሉ አምኖ ለመቀበልም ዝግጁ ነበር። ይሁን እንጂ ዛሬ በገቢውም ሆነ በውሎው እርካታ የሚያገኝበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ዘርአይ ከበርካታ ሰዎች ጋር እንደመገናኘቱ የተለያዩ ልምዶችን አዳብሯል። ከሁሉም ግን በተሰማራበት የሙያ መስክ ደንበኞችን እንዴት መያዝ እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል።

አንድ ቀን በዘርአይ ቤት እንዲህ ሆነ። በየጊዜው ቤቱን ከሚጎበኙ ደንበኞች መሀል አይቷቸው የማያውቅ እንግዶች ቡና ሊጠጡ ወደ እሱ ቤት ጎራ ይላሉ። እንግዶቹ በዛው ህንፃ ላይ ከሚገኝ አንድ ጸጉር ቤት ለመዋብ የመጡ ሁለት ሴቶች ነበሩ። እንደተለመደው አስተናጋጇ ቡናውን ከቁርስ ጋር አዘጋጅታ ለመቅዳት ተዘጋጀች። ትኩሱ ቡና ከመንቆርቆሩ በፊት ግን የሁለቱም እጆች ፈጥነው በስኒዎቹ ላይ አረፉ። ወዲያውኑም ቀጭኑን ትዕዛዝ አስተላለፉ።

ሴቶቹ እሷ በያዘችው ሳይሆን ቀይ ቀለም ባለው ስኒ ብቻ መጠጣት እንደሚፈልጉ ኮስተር ብለው ተናገሩ። ይህን ዕውነታ የሰማችው አስተናገጅ በሁኔታቸው ግራ ተጋባች። የደንበኞቹን ፍላጎት የተረዳው ዘርአይ ግን ምርጫቸውን በማክበር የፈለጉት እንዲሆን የፈቀደላቸው ወዲያውኑ ነበር። እንዲህ አይነቶቹ አጋጣሚዎች በንግድ ዓለም ለሚገኝ ሰው የደንበኞችን አያያዝ ለማወቅ እንደሚረዳ ወጣቱ ይናገራል። ዘርአይ የቀድሞ ማንነቱን የሚያውቁ በርካታ ሰዎች በቤቱ ሲስተናገዱ ይውላሉ። ስለማንቱ ያላቸው አክብሮትም ላቅ ያለ ነው። እሱም ቢሆን እንግዶቹን በመልካም ምግባር ተቀብሎ በፈገግታ ሲያስተናግድ መዋሉን ተክኖበታል። ብዙ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች በአካባቢው ሴቶች ቡና ይልቅ የእሱ ገበያ መድራት ያስገርማቸዋል። በአድናቆትም ምክንያቱን ጭምር የሚጠይቁት አይጠፉም። የዘርአይ ምላሽ ግን ሁሌም ቢሆን የተለመደ ነው። «መልካም አቀባበልና ደማቅ ፈገግታ»

አንዳንዴ እንደ ስኒው የቀለም ምርጫ ሁሉ ቡናው ቀጠነ፣ አልያም ወፈረ ሲሉ የሚነጫነጩ ደንበኞች አይታጡም። የሙዚቃ ምርጫም በእነሱ ፍላጎት ብቻ እንዲሆን የሚሹ ጥቂቶች አይደሉም። ይህ ሲሆን ግን ሁሉንም እንደባህርይውና ፍላጎቱ ተቀብሎ ማስተናግድ ግድ ይላል። ዘርአይ ይህ ሥራ የገንዘብ ትርፍ ብቻ ሳይሆን የሰው ሀብትም አስገኝቶለታል። በውሎው የተለያየ ሙያ ካላቸው ሰዎች ጋር ይገናኛል። ክእነሱ የሚያገኘው ዕውቀትና ልምድም የበረከተ ነው።

ገና በአስራ ሁለት አመቱ እናቱን በሞት ያጣው ዘርአይ የቤተሰብ ፍቅር ሳስቶበት እንዳደገ ይሰማዋል። ያለፈበት አዳጋች የህይወት መስመርም በሌሎች እንዳይደገም የሚጨነቀው ከልቡ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ በስሩ ቀጥሮ ለሚያሠራቸው ሠራተኞች ስሜት እንዲጠነቀቅ ምክንያት ሆኖታል። ከእነሱ ጋር ያለው ግንኙነት የአሠሪና ሠራተኛ ብቻ ሳይሆን ፍቅርና መከባበር የተመላበት ጭምር ነው።

ወጣቱ ዘርአይ ትላንት በጋዜጠኝነት ዓለም፤ ዛሬ ደግሞ በጀበና ቡና ንግድ ላይ ተሰማርቶ ህይወትን መምራት ቀጥሏል። በእሱ ዕምነት ግን አሁን ያለበት ሥራ የመጨረሻ ግቡ አይደለም። ወደፊት ደግሞ ካለበት ከፍ ብሎ ንግዱን ማስፋፋት ይሻል። ዘርአይ በጋዜጠኝነት ሙያ ከመሰማራቱ አስቀድሞ ከነበረው ልምድ በመነሳት የእግር ኳስ ተጨዋች እንደሚሆን የሚገምቱ በርካቶች ነበሩ።

ወደ ሚዲያው ከገባ በኋላም በሙያው ልቆ እንደሚገፋ ታምኖበት ነበር። ዛሬ ባለበት ሥራ ላይ እንዲህ ቢገኝም የነገ ዕቅዱ ወዴት እንደሚያደርሰው የሚወስነው ደግሞ በውሰጡ ያለው ጥንካሬ ብቻ ይሆናል። ሁሌም የሥራ ክቡርነትን የሚያምነው ዘርአይ ለሥራው ተገዢ ሆኖ ማገልገልን ለምዶታል። ማፅዳትና መጥረግ ካለበት ሌሎችን አይጠብቅም። ትላንት ብዕር የጨበጡ ጣቶቹ ዛሬ ለጉልበት ሥራም ሰንፈው አይታዩም።

ዘርአይን ተሰናብቼ ከዘመናዊው ህንፃ ወጣሁ። አይኖቼ መልሶ የጀበና ቡና ከደረደሩ ሴቶች ላይ አረፈ። ይህም ብቻ አይደለም። ከአንዱ ጥግ ተቀምጠው በቡታጋዝ ጭስ እየታወዱ ሻይቡናን አፍልተው በፔርሙስ ይዘው የሚዞሩትን ጭምር ተመለከትኩ። እንደ ወይዘሮ ዘሪቱ በላስቲክ ጎጆ እንደሚገኙትና እንደወጣቱ ዘርአይ ጽዱ በሚባል ሥፍራ እንዳሉት ሁሉ ከጎዳና የማይጠፉት እነዚህ ባለቡናዎች በሥራ ክቡርነት የሚያምኑ ናቸው። በተለይ የተመቻቸ የገበያ ቦታን ቢያገኙ የተሻለ ህይወትን ይመሩ እንደነበር ተሰማኝ። እነሱም በመልካም ፈገግታ ደንበኞቻቸውን «አርሂቡ» ማለትን ያወቁበታልና።

 

 

 

Published in ማህበራዊ

 

ሐምሌ 5 ቀን 2009 .ም ታትሞ በወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ፤ "የፈዴራል ሥርዓት እና የዋና ከተማ አመራረጥ" በሚል ርዕስ ዘርዘር ያለ ጽሑፍ ለንባብ ማቅረቤ የሚታወስ ነው። በወቅቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበው ረቂቅ አዋጅን የማግኘት ዕድሉ ስላልነበረኝ አጠቃላይ ጉዳዮች ዙሪያ የተወሰኑ ሃሳቦችን ያቀረብኩ ሲሆን፤ በቀጣይ ዝርዝር ጉዳዮችን በማንሳት ሃሳቤን ለማቅረብ ቃል መግባቴም የሚታወስ ነው። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ ቅጂ አግኝቼ ያነበብኩ ከመሆኑም በላይ ይህ ረቂቅ አዋጅ ከመዘጋጀቱ በፊት መነሻ ይሆን ዘንድ በኦሮሚያ ክልል ተዘጋጅቶ የቀረበን ጥናታዊ ጽሑፍ የማንበብ ዕድል በማግኘቴ በጉዳዩ ዙሪያ ሰፋ ያለ አስተያየት ለመስጠት በእጅጉ ረድቶኛል።

ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ በመሆኑ በጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስተያየታቸውን የሚሰጡበት መድረክ መዘጋጀት በእጅጉ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። መድረኮች ተዘጋጅተው የተለያዩ አስተሳሰቦች የመንሸራሸር ዕድል ማግኘታቸው በጉዳዩ ዙሪያ ያሉ የተዛቡ አመለካከቶችን በማጥራት ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ከማድረጉም በላይ አዋጁ የተሟላ ቅርፅ ይዞ እንዲወጣ በግብዓትነት የሚያገለግሉ አስተሳሰቦችን ለማሰባሰብም ይረዳል።

በአጠቃላይ ከላይ ያነሳኋቸው ሃሳቦች እንደ መነሻ እንዲያዙ እየጠየቅሁ ወደ ዋናው ፍሬ ነገር ስንመለስ፤ ይህ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም ረቂቅ ህግ በሚል ተዘጋጅቶ የቀረበው ሰነድ ላይ ያለኝን አስተያየት ከማቅረቤ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ጉዳዩን አስመልክቶ የወጡ ሕገ መንግሥቶች፣ አዋጆች እና ደንቦች ያሠፈሯቸውን ድንጋጌዎች እና አንደምታቸውን ፍተሻ እናድርግ።

በፌዴራል መንግሥቱ የተዘጋጁ

የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር

መስተዳድሮችን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 7/1984 አንቀፅ 3(1) ክልል 4 የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር መሆኑን ደንግጓል፤ አዋጅ ቁጥር 7/1984 አንቀፅ 3(4) ደግሞ ክልል 13 (የሐረሪ ብሔረሰብ ወይም የሐረር ከተማ) እና ክልል 14 (አዲስ አበባ) የኦሮሚያ ልዩ ብሔራዊ ጥቅምና ፖለቲካ መብት በእነዚህ ክልሎች ላይ የተጠበቀ መሆኑን ደንግጓል።

ይህ የሽግግር መስተዳድሮችን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ አዲስ አበባ በክልል ደረጃ የመደበ እና ተጠሪነቱም ለማዕከላዊው የሽግግር መንግሥት ሆኖ የመስተዳድሮቹን ግንኙነት በዝርዝር ህግ እንደሚወስን የደነገገ ነበር። በወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ብሔራዊ ጥቅም እና የፖለቲካ መብት በአዲስ አበባ እና በሐረሪ ክልል ላይ እንደሚኖረው ተደንግጎ ነበር። በመሆኑም አዋጁ በቅርፅ እና በይዘት በቀጣይ ከወጡ ድንጋጌዎች መጠቅ ያለና ለአዲስ አበባም ክልላዊ መንግሥት አቋም እንዲኖራት ያደረገ ነበር።

ከዚህ አዋጅ ድንጋጌ መረዳት እንደሚ ቻለው የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ እና በሐረር ከተማ ላይ ልዩ ብሔራዊ ጥቅም እና የፖለቲካ መብት እንዲኖረው መደረጉ በሁለቱ የክልል ከተሞች መስተዳድር ውስጥ የመመረጥ ወይም የሥልጣን ተጋሪነትን የሚያካትቱ ፖለቲካዊ መብቶችን ጭምር ሊኖረው እንደሚችል የሚያመላክት ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያ ሕገ-መንግሥት

የኢፌዼሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ (1) አዲስ አበባን የፌዴራል መንግሥት ርዕሰ ከተማ መሆኗን የደነገገ ሲሆን፤ ደረጃዋም በከተማ አስተዳደር እንዲሆን አደረገ።

በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ (5) መሠረት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም እና የመሳሰሉ ጉዳዮችን በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል በሚል ተደንግጓል።

የሕገ-መንግሥቱ ይህ ድንጋጌ የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ለማቋቋም ከወጣው አዋጅ ቁጥር 7/1984 በተለየ መልኩ አዲስ አበባን ከክልላዊ መንግሥትነት ወደ ከተማ አስተዳደርነት ዝቅ አድርጓል። የኦሮሚያ ልዩ ብሔራዊ ጥቅም እና የፖለቲካ መብትን አስመልክቶ የነበረው ድንጋጌንም በአገልግሎት አቅርቦት ወይም በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ደረጃ ሲገድበው፤ ሌሎቹን ደግሞ የመሳሰሉት በሚል በመደንገግ ዝርዝሩን በሕግ እንደሚወስን አስቀምጧል። ስለሆነም በሕገ መንግሥቱ አቀራረፅ መሠረት ጉዳዩ በዝርዝር ህግ እንደሚታይ ቢደነግግም ፖለቲካ መብት የሚለውን በዝምታ ማለፉ የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ለማቋቋም ከወጣው አዋጅ አንፃር ውስንነት ያለው ይመስላል። ከዚህ በተጨማሪ ሕገ-መንግሥቱ ኦሮሚያ በሐረር ከተማ ላይ ያላትን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች በደፈናው ሳያነሳ ያለፈበት ሁኔታም እንዳለ ማየት ይቻላል። የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድርን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ «ልዩ ጥቅም» አስመልክቶ በሽግግሩ ጊዜ «ልዩ ብሔራዊ ጥቅም» በሚል ያሰፈረ ሲሆን፤ በሕገ-መንግሥቱ ላይ ግን «ልዩ ጥቅም» በሚል ብቻ አልፎታል፡፡

በአዲስ አበባ አስተዳደር የተዘጋጁ አዋጆች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 87/1989 አንቀፅ 33 መሠረት የሚከተሉት ድንጋጌዎች ቀርበዋል። የአዲስ አበባ ወሰን በከተማው መስተዳድር እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በጋራ እንደሚወሰን፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫውን አዲስ አበባ የማድረግ መብት እንዳለው፤ መስተዳድሩ በአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚኖሩት የኦሮሚያ ህዝብ የተለያዩ አገልግሎቶችን እንደከተማዋ ነዋሪዎች በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ፤ ከተማ መስተዳድሩ ማናቸውም የክልሉን ህዝቦች የሚነኩ የልማት ሥራዎችን ሲያከናውን በቅድሚያ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመመካከር የሚተገብር ስለመሆኑ የሚደነግገው ይገኝበታል።

አዋጁ ሲገመገም ከተማ መስተዳድሩ ማናቸውም የክልሉን ህዝቦች የሚነኩ የልማት ሥራዎችን ሲያከናውን በቅድሚያ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመመካከር ይተገብራል ከሚለው ውጪ ቀሪዎቹ ልዩ ጥቅም በሚል ሊገለፁ የሚችሉ ሣይሆኑ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መብቶች በመሆናቸው የተለየ ነገር የያዙ አይደሉም። ስለሆነም የከተማ አስተዳደር ቻርተሩ በሕገ-መንግሥት የተቀመጠ ልዩ መብትን በአግባቡ በሚሸፍን መልኩ ተቀርጿል ማለት አያስደፍርም።

የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር ቁጥር 311/995 አንቀፅ 62 መሠረት የከተማው አስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልል ግንኙነትን በሚከተለው መልኩ አስቀምጦታል። የከተማ አስተዳደሩ ከአሮሚያ ክልል ጋር ፍሬአማ የትብብር ግንኙነት እንደሚኖረው፤ በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 49 (5) መሠረት የኦሮሚያ ክልል ጥቅም የተጠበቀ መሆኑን ዝርዝሩም በከተማው አስተዳደር እና በክልሉ መንግሥት መካከል በሚደረግ ስምምነት ወይም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚወጣ ሕግ እንደሚወሰን፤ የከተማ አስተዳደሩ ወሰንን በተመለከተ አሁን ያለው የከተማው ክልል እንደተጠበቀ ሆኖ የከተማው አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል ጋር በሚደረግ ስምምነት ወይም በፌዴራል መንግሥት ይወሰናል በሚል ደንግጓል።

ይህ የከተማ መስተዳድር ቻርተር ማሻሻያ ከቀዳሚው የከተማው ቻርተር አዋጅ ቁጥር 87/1989 በተለየ መንገድ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም የሚለውን «ጥቅም» በሚል ብቻ ደንግጓል። በሌላ በኩል ከቀዳሚው የከተማ መስተዳድሩ አዋጅ ቁጥር 87/1989 በተለየ መንገድ የከተማ አስተዳደሩ እና የኦሮሚያ ክልል በጋራ የወሰን ክልል ያስቀምጣሉ የሚለውን ተጨማሪ አካል በጉዳዩ እንዲገባ የሚያደርግ ድንጋጌ አካትቶ ወጥቷል። በዚህም መሠረት የፌዴራል መንግሥት የሁለቱን ስምምነት ሳይጠይቅ የአዲስ አበባ ከተማን ወሰን የመለየት እና የመወሰን ሥልጣን እንዲኖረው የሚያስችል የሕግ ድንጋጌ በማሻሻያ አዋጁ ላይ ማካተቱ በጉድለት የሚቀመጥ ነው።

ለሦስተኛ ጊዜ የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995 የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ግንኙነትን በተመለከተ የተለየ ለውጥ ሳያደርግ ከነጉድለቱ አዋጅ ቁጥር 311/1995 ላይ ያለውን እንዳለ አስፍሯል።

በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የወጡ አዋጆች

በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የወጡ ሕጐች ደግሞ አዲስ አበባን በተመለከተ የተለያዩ ይዘት ያላቸው አዋጆችን በማውጣት እንዲሁም ማሻሻያዎችን በማድረግ የተቀረፀ ሲሆን፤ ይህም በዋነኛነት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ ፊንፊኔ መሆኑን በመደንገግ ረገድ የቀረበው ብቻ ነበር። በዚህም ሠረት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድር ሕገ-መንግሥት አዋጅ ቁጥር 2/1985 አንቀፅ 58 ሥር የክልሉ ዋና ከተማ ፊንፊኔ መሆኑን የተደነገገበት ቀዳሚው ነበር።

የሽግግሩ ወቅት ተጠናቅቆ በ1987 የፀደቀው ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 6 ሥር የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ ከተማ ፊንፊኔ መሆኑን እንደ መጀመሪያው ሕገ-መንግሥት ደንግጐ ነበር። ለሦስተኛ ጊዜ የተሻሻለው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሕገ-መንግሥት አዋጅ ቁጥር 46/1994 አንቀፅ 6 መሠረት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ ከተማ አዳማ መሆኑን ደንግጓል። ከሦስት አመት በኋላ በ1997 በተካሄደው የጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤ የ1994 ሕገ-መንግሥት ማሻሻያን ውድቅ በማድረግ በአዋጅ ቁጥር 94/1997 አንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ 3 መሠረት የኦሮሚያ ዋና ከተማ ፊንፊኔ እንዲሆን ወስኗል።

ከእነዚህ የዋና ከተማ መቀመጫን አስመልክቶ ከተደነገገው ውጪ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅምን አስመልክቶ በኦሮሚያ ሕገ-መንግሥት ላይ ሠፍረው የሚገኙ የሕግ ድንጋጌዎች የሌሉ ሲሆን በ2000 .ም የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ማቋቋሚያ ደንብ ተዘጋጅቶ መቅረቡ ይታወቃል።

ይህ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አስተዳደር ምክር ቤት (ካቢኔ) የተዘጋጀው ደንብ ቁጥር 115/2000 የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መስተዳድር ጽህፈት ቤትን ያቋቋመ ሲሆን፤ ተግባሩን አስመልክቶ በአንቀፅ 9 ንዑስ አንቀፅ 2 መሰረት ከፊንፊኔ ከተማ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት መሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጥናት በማካሄድ የመፍትሄ ሃሳብ ለሚመለከተው አካል እንደሚያቀርብ ሲፀድቅም ሥራ ላይ እንዲውል እንደሚያደርግ ደንግጓል።

ከዚህ በተጨማሪ በአንቀፅ 9 ንዑስ አንቀፅ 6 መሠረት የፊንፊኔ ከተማ እና የኦሮሚያ ድንበር ተለይቶ እንዲታወቅ ለልዩ ዞን ጽህፈት ቤቱ ከተሰጡት ተግባራት ጋር የሚካተት ነው። ይሁን እንጂ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ወቅት ከተሞቹ ከልዩ ዞኑ በመውጣታቸው ይህ ደንብ ተፈፃሚነት ሊያገኝ እንደማይችል መገንዘብ ይቻላል።

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣው ረቂቅ አዋጅ

በረቂቅ አዋጁ ክፍል አንድ የአዋጁን ትርጓሜ በሚደነግገው አንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ 4 ሥር «ልዩ ጥቅም» ለሚለው ቃል የተሠጠው ትርጉም «በሕገ-መንግሥቱ ዕውቅና ያገኙ የአገልግሎት አቅርቦት፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም እና የመሳሰሉት እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ናቸው» በማለት ያስቀመጠ ሲሆን፤ ይህ ትርጉም ከሕገ-መንግሥቱ ምንም ሳይጨመርበት እና ሳይቀነስ እንዳለ ተገልብጦ የሠፈረ በመሆኑ የዝርዝር ሕግ ቁመናና ባህሪይ እንዲይዝ አድርጐታል ማለት አይቻልም። ልዩ ጥቅሙን በአገልግሎት አቅርቦት እና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ዙሪያ እንዲታጠር ማድረጉም ሠፋ ያሉ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ መሠል መብቶችን ሳያካትት ውስን በሆነ መልኩ እንዲቀረፅ አድርጐታል። ስለሆነም ለአዋጁ መውጣት መሠረታዊ ምክንያት የሆነው ሕገ-መንግሥቱን በዝርዝር የማብራራት እና የማፍታታት ተልዕኮውን መወጣት ያልቻለ ረቂቅ አዋጅ በመሆኑ የተወካዮች ምክር ቤት ለጉዳዩ አፅንኦት በመስጠት ሊፈትሸው ይገባል።

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ክፍል አንድ አንቀፅ 3 ላይ የተፈፃሚነት ወሰን በሚለው ሥር «ይህ አዋጅ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እና እንደ አግባቡ በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ተፈፃሚነት ይኖረዋል» ይላል። ይህ አንቀፅ ግልፅነት የሚጐድለው በሌላ አገላለጽ የአዋጁን መንፈስ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣ አዋጅ ሆኖ ሳለ፤ ነገር ግን በኦሮሚያ ክልል እና በክልሉ ነዋሪ አርሶ አደሮች ላይ አዋጁን የማስፈፀም ግዴታ መጣሉ ልዩ ጥቅም ሳይሆን ልዩ ግዴታ ተደርጐ እንዲወሰድ ሊያደርገው ይችላል።

የአዋጁ ክፍል ሦስት አንቀፅ 8 ደግሞ ለአዲስ አበባ ከተማ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን አስመልክቶ ያሠፈረው ጉዳይ አለ። ይሄውም የኦሮሚያ ክልል ከግዛቱ ሥር ከሚገኘው የከርሰ ምድር እና የገፀ-ምድር የውሃ ሀብት ለአዲስ አበባ የማቅረብ ግዴታን የሚያመላክት በመሆኑ (ወጪው በአዲስ አበባ አስተዳደር የሚፈፀም መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ) የኦሮሚያ ክልል የሚያገኘው ልዩ ጥቅም ነው በሚል ማስቀመጥ ተገቢነት አለው ማለት አይቻልም።

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልልን ግንኙነት አስመልክቶ ከሽግግር ወቅት ጀምሮ የወጡ ሕገ-መንግሥቶች፣ አዋጆች እና ደንቦች በጥልቀት ለተመለከታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ የነበራቸው ቁመናን እያጡ የፌዴራላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ሥር የሚመሠረቱ የፌዴሬሽኑ አካላት ግንኙነቶችን ሥርዓት ማስያዝ እንዳልተቻላቸው መገንዘብ ይቻላል። በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ዕምነት የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 7/1984 የተሻለ ቁመና የነበረው በሂደትም ወደ ተሻለና በተግባራዊ እንቅስቃሴ ከሚቀሰሙ ልምዶች በመታገዝ እየዳበረ ውጤት ሊያስገኝ ወደሚችል አቅጣጫ ማሸጋገር የሚቻል እንደነበር ያምናል። ከዚህ ውጪ የወጡት የተለያዩ ህጐች እርስ በእርሳቸው የሚቃረኑ መሠረታዊው የፌዴራል ሥርዓቱን ዋና ከተማ በማደራጀት ረገድ አቅም ያልነበራቸው በየጊዜው በማሻሻያ እየተደረቱ ውጤት ላይ ለመድረስ አለመቻላቸውን ከላይ የቀረቡትን የህግ ድንጋጌዎች በመመልከት መታዘብ ይቻላል። አሁን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተዘጋጅቶ የቀረበው የሕግ ረቂቅም እንደዚሁ የችግሩን ምንጭ ተገንዝቦ መፍትሄ ሊያመጣ በሚችል መልኩ መዘጋጀት ካለመቻሉም በላይ የቀደምት አዋጆች ተቀጥላ በመሆኑ በዝርዝር ሊፈተሽ ይገባዋል።

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተዘጋጅቶ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ያነሳኋቸው ሦስት ዋና ዋና ጉድለቶች መነሻ ምንጭ አዲስ አበባ ከተማ ለፌዴራል ሥርዓቱ ዋና ከተማ ከመሆኗ ጋር በተያያዘ እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ተዳምረው የከተማዋ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ወሰኖች (Political boundary versus economic boundary) መካከል የወለዱት ነው የሚል አስተያየት በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ዘንድ አለ።

የአዲስ አበባን እና የኦሮሚያን ክልል ወሰን ለመወሰን እየታሰበ ያለበት ሁኔታ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ብቻ የሚያይ መሆኑና የከተማዋ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ደግሞ ከፖለቲካው የወሰን ድንበር ዘልቆ የመውጣት ፍላጐት የማሳየቱ ቅራኔ በረቂቅ አዋጁ ላይ «የአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ» የሚለውን ትርጉም ሲያስቀምጥ ፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞንን አካትቶ የመያዝ መንፈስ እንዳለው መገንዘብ ይቻላል። «የልዩ ጥቅምን» አስመልክቶም ትርጉም ሲያስቀምጥ የአገልግሎት አቅርቦት እና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም በሚል ሲያልፈው መሠረታዊ የሆኑ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የፖለቲካ እና ሌሎች መብቶችን አለማካተቱ የረቂቅ አዋጁ ቁልፍ ችግሮች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ።

በመሠረቱ ይህን የመሰሉ ችግሮች የአዲስ አበባ ከተማ ብቸኛ ችግር ሣይሆን በመላው ዓለም ያሉ በተለይ የፌዴራል ሥርዓትን የሚከተሉ አገሮች ዋና ከተሞች የሚገጥማቸው ፈተና ነው። በመሆኑም በቀጣይ የአዲስ አበባ ከተማ የፌዴራል መንግሥቱ ዋና መቀመጫ ከመሆኗ ጋር በተያያዘ ያለባት ችግር እና መፍትሄም ሊሆን ይችላል የምለው ሃሳቦችን በማካተት እንዲሁም ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እጅግ ተመሳሳይነት ያላት የቤልጅየም ተሞክሮን ከዋና ከተማዋ ብራሰልስ አንፃር በማነፃፀር ለማቅረብ እሞክራለሁ።

ከእነዚህም ሊወሰዱ የሚችሉ ልምዶችን በመቀመር ከኢትዮጵያ እና ከአፍሪካ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር በማጣመር ረቂቅ አዋጁን ምሉዕ የማድረግ ተግባር ደግሞ የአገሪቱ ምሁራን ዋነኛ ተግባር መሆን ይገባዋል። ዩኒቨርሲቲዎቻችንም በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት እና ምርምር በማድረግ ለረቂቅ አዋጁ ግብዓት እንዲያቀርቡ መንግሥት ልዩ ትኩረትና ድጋፍ እንዲሁም ማበረታቻ በማድረግ ለጉዳዩ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መፍትሄ እንዲቀርብ መሥራት ይጠበቅበታል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም በክልሉ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችን በመጠቀም የተደራጀና የተሟላ ጥናት ይዞ በመቅረብ በጉዳዩ ላይ ተዋናኝ መሆን ይኖርበታል።

 

ሮባ ቶኪቻው

 

Published in ፖለቲካ

መንግሥት ቀደም ሲል በገጠር ለሁለት አስር ዓመታት ያህል የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር ተግባራዊ ሲያደረግ ቆይቷል፡፡ በዚህም መርሀ ግብር በርካታ በገጠር የሚኖሩ የህበረተሰብ ክፍሎች በምግብ ራሳቸውን የቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ከዚህ በመነሳት ይህንን መርሀ ግብር በከተሞችም እንዲተገበር ማድረጉን የፌዴራል የሥራ ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ተጠባባቂ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን አሰፋ ይናገራሉ፡፡ ከአቶ ሰለሞን ጋር በከተሞች የምግብ ዋስትና አተገባበር ዙሪያ ቃለ መጠየቅ አድርገናል፡፡ ሙሉ መረጃውን እነሆ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የከተሞች የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር ትግበራ ምን ደረጃ ላይ ነው?

አቶ ሰለሞን፡- የከተሞች የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር መነሻው አገሪቱ ውስጥ ያለውን የህብረተሰብ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፡፡ መንግሥት ቀደም ሲል በገጠር ለሁለት አስር ዓመታት ያህል የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር ተግባራዊ ሲያደረግ ቆይቷል፡፡ በዚህ መርሀ ግብርም በርካታ በገጠር የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በምግብ ራሳቸውን የቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ከዚህ በመነሳት ይህንን መርሀ ግብር በከተሞችም እንዲተገበር አድርጓል፡፡ ለዚህ ማስፈፀሚያም በ2008 .ም የከተሞች የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር ስትራቴጂ ወጥቷል፡፡ የ10 ዓመት የከተሞች የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር ዕቅድ ተይዟል፡፡ ይህም መሰረት ያደረገው እኤአ በ2011 የድህነት መጠንን የሚያሳየውን የማዕከላዊ ስታስቲክስ ጥናት ነው፡፡

በዚህ ጥናት መሰረት በከተሞች ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩት አራት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዜጎች ናቸው፡፡ እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ነው በመርሀ ግብሩ አማካኝነት በአስር ዓመት ውስጥ ተጠቃሚ ለማድረግ የታቀደው፡፡ የዚህ መርሀ ግብር የመጀመሪያው ዙር በ2009 .ም አጋማሽ ላይ በተመረጡ በ11 ከተሞች ተጀምሯል፡፡

የመጀመሪያው መርሀ ግብር ለአምስት ተከታታይ ዓመት የሚቆይ ነው፡፡ በመርሀ ግብሩ 70 በመቶ የሚሆነው በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሲሆን ቀሪው 30 በመቶ በሌሎች ከተሞች ላይ ያተኩራል፡፡ ስለዚህ ዘጠኙ ክልሎች በመረጧቸው ከተሞችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች መርሀ ግብሩ ተፈፃሚ ሁኗል፡፡ በዚህ መሰረት በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በመቀሌ፣ በጋምቤላ፣ በደሴ፣ በጅግጅጋ፣ በሀዋሳ፣ በአዳማ፣ በሐረር፣ በሠመራና በአሶሳ ከተሞች የሚኖሩ የድሀ ድሀ ተብለው የተለዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመርሀ ግብሩ ተጠቃሚ እየሆኑ ናቸው፡፡

ለምግብ ዋስትና መርሀ ግብሩ በተሠራው ድጋፍ የማፈላለግ ሥራ ከዓለም ባንክ በብድር 300 ሚሊዮን ዶላር ሲገኝ ከመንግሥት ደግሞ 150 ሚሊዮን ዶላር ተመድቧል፡፡ በአጠቃላይ ለአምስት ዓመቱ መርሀ ግብር 450 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተይዞለታል፡፡

የምግብ ዋስትናውን ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ለማስተሳሳር ሲባል ቀደም ሲል ጥቃቅና አነስተኛ ኤጀንሲ የሚባለው በአዲስ መልኩ የምግብ ዋስትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ኤጀንሲ ተብሎ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 374/3008 .ም በፌዴራል ደረጃ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ በተዋረድ በየክልሎችም ኤጀንሲዎችና ጽሕፈት ቤቶች ተከፍተዋል፡፡ የሰው ኃይልን የማሰልጠንና ቢሮዎችን የማደራጀት ሥራ ከ2009 .ም ጀመሮ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የሚመለከታቸው አካላትም በመርሀ ግብሩ ዓላማና አተገባበር ዙሪያ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ተደርጓል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በመርሀ ግብሩ የሚካተቱ ዜጎች ምልመላ በምን መልኩ ነው የተካሄደው?

አቶ ሰለሞን፡- የጠቀስኳቸው ሥራዎች ተሠርተው ወደ ትግበራ ሲገባ በከተሞች ያላግባብ የመጠቀም ፍላጎት የሚታይ በመሆኑ ይህንን ለመግታት ሲባል የተጠቃሚዎች የምልመላ ሥርዓት ላይ የአሠራር መመሪያ ማዘጋጀት ተችሏል፡፡ በዚህ መሰረት የተጠቃሚዎች ምልመላ የተከናወነው በየአካባቢው ህዝቡ ተሰብስቦ ዕከሌ ገለልተኛ ሆኖ ሊመርጥ ይችላል ተብለው በተመረጡ መልማይ ኮሚቴዎች አማካኝነት ነው፡፡

ለምሳሌ የምግብ ዋስትና መርሀ ግብሩ በአዲስ አበባ በመጀመሪያ ዙር በ35 ወረዳዎች ላይ ነው የተተገበረው፡፡ በእነዚህ ወረዳዎች በየቀጣናውና በየመንደሩ መልማይ ኮሚቴ አባላት ተመረጡ፡፡ ኮሚቴዎቹ ቤት ለቤት በመሄድ ድሀም ይሁን ሀብታም ሁሉንም ነዋሪ መዘገቡ፡፡ በመመዘኛ መስፈርቶቹ መሰረት የድሀ ድሀ፣ መካከለኛና ሀብታም ተብሎ በአራት ደረጃ ተሰጥቷል፡፡ እናም በየአካባቢው የድሀ ድሀ ተብለው የተመረጡ ሰዎች መርሀ ግብሩ እጩ ሆነው ይቀርባሉ፡፡ እነ እከሌ የዚህ መርሀ ግብር ተጠቃሚ ናቸው ተብሎ ስም ዝርዝራቸው ይለጠፋል፡፡ ማንም ሰው ተጠቃሚ መሆን አለብኝ አልያም እሱ ተጠቃሚ መሆን የለበትም የሚል ቅሬታ ማቅረብ ይችላል፡፡ ቅሬታ ሰሜ ኮሚቴ መልስ ይሰጣል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ሰዎች የፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሚሆኑት፡፡

የቀጣናው ኮሜቴ ከወረዳው አስተዳደር፣ በየደረጃው ካሉ የቴክኒክ ኮሚቴዎች ጋር ተናቦ ከሠራ በኋላ ትክክለኛ ምርጫ መካሄዱን ይወሰናሉ፡፡ የሚስተካከል ነገር ካለ ይስተካከላል፡፡ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የድህነት አመላካቾችን በመጠቀም መመዘን የሚችል አማካሪ ድርጀት ተቀጥሯል፡፡ ከዓለም ባንክ አማካሪዎች ጋር በመሆን ከተመረጡት 10 በመቶ ያህሉን በናሙና መልክ በመውሰድ ትክክለኛ የድሀ ድሀ ናቸው ወይስ አይደሉም የሚል የኑሮ ደረጃ ምዘና ያካሄዳሉ፡፡ በዚህ መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ በጥሩ ሁኔታ ምልመላው ተካሄዷል፡፡

ቀድመው ወደ ሥራ በገቡት ደሴና መቀሌ ከተሞች ላይ ግን ከምልመላው ጋር በተያያዘ የተለያዩ ችግሮች አጋጥመዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ድጋሚ ምልመላ እንዲካሄድ ተደርጎ ተስተካክሎ ማረጋጋጫ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ስለዚህ ቀደመው ከገቡት ከተሞች ትምህርት ተወስዶ ሀዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ አዳማ፣ ጅግጅጋ፣ ጋምቤላና አሶሳና አዲስ አበባ ከተሞች ጥንቃቄ በመደረጉ ያለዳግም ምልመላ የተመለመሉት ተቃባይንትን አግኝተዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በመርሀ ግብሩ ተጠቃሚ ለመሆን የተመለመሉት ድጋፉ የሚሰጣቸው እንዴት ነው?

አቶ ሰለሞን፡- ተጠቃሚዎቹ ከተመረጡ በኋላም በሁለት ተከፍለዋል፡፡ መሥራት የሚችሉት ሰዎች ሠርተው ነው ድጋፉን የሚያገኙት፡፡ መሥራት የማይችሉት ደግሞ ቀጥታ ድጋፍ ያገኛሉ፡፡ ሌላው አሁን ተግባራዊ ያልሆነው ልዩ ድጋፍ የሚካተቱት ሴተኛ አዳሪዎችና በልመና የሚተዳደሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ከዚህ ዓመት አጋማሽ ጀምሮ በመርሀ ግብሩ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

በቤተሰብ ደረጃ አንድ ሰው መሥራት የሚችል ከሆነ በአካባቢ ልማት ሥራ ይሳተፋል፡፡ በቤተሰብ ውስጥ ያሉት አካል ጉዳተኞች፣ ህፃናትና አቅመ ደካማ ከሆኑ በቀጥታ ድጋፍ የሚያገኙ ይሆናል፡፡ ይህንንም የሚወስነው ሰፈራቸው ያለው መልማይ ኮሜቴ ነው፡፡

መርሀ ግበሩ በታሰበው ጊዜ ሳይሆን ሦስት ወር ዘግይቶ ነው የጀመረው፡፡ ከገጠሩ ምግብ ዋስትና የወሰድናቸው ልምዶች ተነስተን ማስተካከል የሚገባን ጉዳዮች ነበሩ፡፡ አንዱ ጉዳይ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ ስለዚህ የክፍያ ሥርዓቱ በንግድ ባንክ አማካኝነት የሚፈፀም ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአገር አቀፍ ደረጃ በከተሞች የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር ምን ያህል ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ?

አቶ ሰለሞን፡- ለመርሀ ግብሩ 450 ሚሊዮን ዶላር ተመድቧል፡፡ በዚህም 604 ሺሀ ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 22 ሺ ሰዎች ደግሞ በልዩ ድጋፍ በጎዳና የሚኖሩና ቤተሰብ የሌላቸው ናቸው፡፡ በሦስት ዙር ነው ተጠቃሚዎች የሚመለመሉት፡፡ በዓመት 190 ሺ ሰዎች ናቸው ተጠቃሚ የሚሆኑት፡፡

ከዚህ ውስጥ 123 918 የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ በተመረጡት 10 ከተሞች የሚገኙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በመጀመሪያው ዙር ድሬዳዋ 12 ሺህ፣ ሀዋሳ 11 ሺህ፣ አዳማ ስምንት ሺህ፣ ደሴ ስድስት ሺህ፣ መቀሌ አምስት ሺህ፣ ጅግጅጋ አምስት ሺህ፣ ጋምቤላ አምስት ሺህ 52፣ አሶሳ ሦስት ሺህ 750 እና ሠመራ አንድ ሺህ 500 ሰው ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ በጥቅሉ ባለፈው ዓመት በመርሀ ግብሩ 190 ሺሀ ሰዎች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከተሞቹስ የተመረጡበት መስፈርት ምንድነው?

አቶ ሰለሞን፡- ከተሞቹን የመረጡት ራሳቸው ክልሎቹ ናቸው፡፡ እኛ ያደረግነው በክልላቸው ከሚገኙት ከተሞች ውስጥ ባላቸው የድህነት ስፋት አኳያ መርጠው እንዲሰጡን ነው፡፡ የእነሱን ምርጫ ነው አክብረን ሥራውን የጀመርነው፡፡ በመጀመሪያው ዙር 11 ከተሞች ናቸው እንደ ሠርቶ ማሳያ የተመረጡት፡፡ ከደሴ ውጭ አብዛኛዎቹ የክልሎቹ ዋና ከተሞች ናቸው፡፡ ወደፊት በመርሀ ግብሩ 912 ከተሞች ናቸው የሚካተቱት፡፡

አዲስ ዘመን፡- በመርሀ ግብሩ ምን ያህል ሰዎች ቀጥታ ድጋፍ ያገኛሉ?

አቶ ሰለሞን፡- ከመርሀ ግበሩ 84 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች በአካባቢ ልማት ተሳትፈው ነው ተጠቃሚ መሆን ያለባቸው፡፡ ስለዚህ 190 ሺህ የመርሀ ግብሩ ተጠቃሚዎች ውስጥ 159 ሺህ 600 በአካባቢ ልማት ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ 30 ሺህ 400 ደግሞ በቀጥታ ድጋፍ ያገኛሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- አንድ ሰው በዚህ መርሀ ግብር ምን ይህል ድጋፍ ያገኛል?

አቶ ሰለሞን፡-የተጀመረው መርሀ ግብር ለግለሰብ የሚሰጥ ሳይሆን ቤተሰብን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ለምሳሌ አራት ወይም ከዚያ በላይ ቁጥር ያለው ቤተሰብ ከሆነ በአካባቢ ልማት ከተሳተፈ በአንድ ወር እስከ አንድ ሺህ 200 ብር ያገኛል፡፡

በወር 20 ቀን በአካባቢ ልማት ሥራ ይሠራል ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው በወር 5 ቀን ሠርቶ በወር 300 ብር ያገኛል፡፡ በቀን 60 ብር ነው የሚታሰብላቸው፡፡ በየወቅቱ እየተጠና የሰው ኃይል ዋጋ ሲጨምር አብሮ የሚቀየር ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ቤተሰብ የሌለው ሰው የመርሀ ግብሩ ተጠቃሚ አይሆንም ማለት ነው?

አቶ ሰለሞን፡- የሚያገኘው ድጋፍ ይቀንሳል እንጂ አንድም ሰው በመርሀ ግብሩ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ በወር አምስት ቀን ብቻ ሠርቶ 300 ብር ያገኛል፡፡ ቀሪውን ቀን የሚፈልገውን ሥራ መሥራት ይችላል፡፡ ይህ 300 ብር የሚሰጠው የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ ነው፡፡ በቀጥታ ተጠቃሚ የሚሆነው ደግሞ በወር ለአንድ ሰው 170 ብር ያገኛል፡፡ በስሙ የባንክ ሂሳብ ይከፈትለታል፡፡ በየወሩ ድጋፉን ከባንክ የሚወስድ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በመርሀ ግብሩ ከሚሰጠው ገንዘብ በተጨማሪ የሚያገኙት ድጋፍስ ይኖር ይሆን?

አቶ ሰለሞን፡- የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ሂደት ላይም ቢሆን ነፃ ህክምና ትምህርት ያገኛሉ፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚኖሩት የመርሀ ግብሩ ተጠቃሚዎች ነፃ ትራንስፖርትም እንዲያገኙ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገርን እንገኛለን፡፡ ስለዚህ ወሳኝ የሆኑ የማህበራዊ አገልግሎቶችን አብሮ የማቅረብ ሥራ ይሠራል፡፡

አዲስ ዘመን፡-ምን አይነት የአካባቢ ልማት ሥራዎችን ናቸው የሚሠሩት?

አቶ ሰለሞን፡-ይህ የከተሞች የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር ነው፡፡ ስለዚህ የአካባቢ ልማት ሥራዎቹ ከተሞችን ፅዱ፣ ውብ፣ ለነዋሪዎች ምቹና ከተለያዩ አደጋዎች መከላከል አኳያ የተቃኘ ነው፡፡ አምስት ሥራዎች ተመርጠዋል፡፡ የመጀመሪያው ደረቅ ቆሻሻን ማሰባሳብ፣ መለየትና እሴት ጨምሮ መጠቀም ነው፡፡ ሁለተኛው አካባቢን አረንጓዴ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ማለት የመንገድ አካፋዮችን፣ የመንገድ ዳሮችንና ፓርኮችን ማልማት የሚያካትት ነው፡፡

ሦስተኛው የተቀናጀ የተፋሰስ ሥራ ነው፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በርካታ መንገዶች ተፋሰስ የሌላቸው በመሆኑ ዝናብ ሲዘንብ መንገዶች ሙሉ ለሙሉ የሚዘጉበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህን ለማስተካከል የከተማ አስተዳደሩ በሚያወጣው ዲዛይን መሰረት የሚሠራ ይሆናል፡፡ አራተኛው ምቹ የግብርና ቦታ መፍጠር ነው፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ብዙ የድንጋይ ማውጫ ቦታዎች ድንጋይና ጠጠር ወጥቶባቸው ጉድጓድ ሆነው ቀርተዋል፡፡ እነዚህ ቦታዎች ላይ ቆሻሻ በመድፋትና በመድፈን ለግብርና ሥራ ማዋል ይቻላል፡፡ እነዚህን ሥፍራዎች ለግብርና ሥራ ምቹ የማድረግ ሥራ ይሠራል፡፡

አምስተኛው የመሰረተ ልማት ሥራ ነው፡፡ በተመረጡና በጣም የድሀ ድሀ በሚባሉ ሰፈሮች ላይ የአካባቢው ህብረተሰብ እንደ ችግር የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ የጋራ መፀዳጃ ቤቶች፣ ድልድይ፣ መብራትና የድንጋይ ንጣፍ መንገድ በወጪ መጋራት ይሠራሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለተጠቃሚዎች ከሚሰጥ ክፍያ በተጨማሪም እነዚህን ሥራዎች ለመሥራት የሚያስችል በጀት ተይዟል?

አቶ ሰለሞን፡- መርሀ ግብሩ ለዚህ ሥራ የካፒታል ወጪዎች አሉት፡፡ ለአዲስ አበባ ለስድስት ወር ብቻ ለዚህ ሥራ 92 ሚሊዮን ብር ተመድቧል፡፡ ገንዘቡ ለመሳሪያዎች ግዥና ለሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች የሚውል ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በመርሀ ግብሩ ተጠቃሚ የሚሆኑት ሰዎች ለምን ያህል ጊዜ ነው?

አቶ ሰለሞን፡- በቀጥታም ሆነ በአካባቢ ልማት ተሳትፈው የመርሀ ግብሩ ተጠቃሚ የሚሆኑት ለሦስት ዓመት ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ከድጋፉ ጎን ለጎን በየዓመቱ ኑሮቸውን በዘላቂነት ማሻሻል የሚችሉበት ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በአካባቢ ልማት ሲሳተፉ እንዲቆጥቡ ይደረጋል፡፡

ለአብነት ያህል የመርሀ ግብሩ ተጠቃሚዎች ከሚያገኙት 20 በመቶ እየቆጠቡ ነው፡፡ ከዚህ መርሀ ግበር ከመመረቃቸው በፊት የቴክኒክና የሥራ አመራር ስልጠና በነፃ ይሰጣቸዋል፡፡ የንግድ ዕቅድም ይሠራላቸዋል፡፡ በመርሀ ግብሩ ለሚመረቁ ሰዎች የሚሰጥውን ገንዘብና የቆጠቡትን ጨምረው እንደ ፍላጎታቸው የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው ወይም ተቀጥረው መሥራት ይችላሉ፡፡

እናም የቤተሰቡን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ሥራ ስለምንሠራ ከቤተሰቡ ውስጥ አንድ ሰው እንዲመርጡ ይደረጋል፡፡ በተመረጠው ሰው ላይ የቤተሰቡን የምግብ ዋስትና እንዲያረጋግጥ የሚያስችሉ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ ሥራ ፈጥሮ ይሰማራል ወይንም ከቴክኒክና ሙያ ሰልጥኖ የሥራ ዕድል እንዲያገኝ ከመንግሥትና ከግል ተቋማት ጋር የሥራ ትስስር ይፈጠርለታል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከተሞች ላይ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሲታሰብ ትልቁ ችግር የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ነው፡፡ ዘላቂ የኑሮ ማሻሻያው ይህንን የማሟላት ዕቅድ አለው?

አቶ ሰለሞን፡- ሰዎቹ በፍላጎታቸው መሰረት በመረጡት የሥራ መስክ እንዲሰማሩ እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን ከወዲሁ ዝግጅት የተደረገበት በከተማ ግብርና ላይ ነው፡፡ ሰዎች በየአካባቢው በከተማ ግብርና እንዲሰማሩና ባላቸው ቦታ ላይ ምርታማ እንዲሆኑ የማድረግ ዕቅድ ይዘናል፡፡ ሌላው የእኛ ኤጀንሲ መደበኛውን ሥራ ዕድል ፈጠራ እየመራ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ የቆጠቡትንና ከመርሀ ግብሩ የሚያገኙትን ገንዘብ ይዘው ሥራ እንፈጥራለን ለሚሉት 20 በመቶ ከቆጠቡትና በመርሀ ግብሩ ሲመረቁ በሚያገኙት ገንዘብ መሸፈን ሲችሉ 80 በመቶ ደግሞ ከአነስተኛ ቁጠባና የብድር ተቋማት ብድር እንዲያገኙ ይደረጋል፤ መሥሪያና መሸጫ ቦታም ይመቻችላቸዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ቀጣይ ዕቅዳችሁ ምንድነው?

አቶ ሰለሞን፡- 2010 .ም መጨረሻ ላይ የመረሀ ግብሩ አፈፃፀም ይገመገምና ይቀጥል አይቀጥል የሚለው በመንግሥት የሚወሰን ይሆናል፡፡ አሁን ባለን መረጃ ግን ሌሎች ከተሞችም በዚህ መርሀ ግብር የመካተት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ መንግሥትም ያለውን ዕድገት ለሁሉም ተደራሽና ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል የሚደረግበት አንዱ መንገድ ይህ ነው፡፡ እናም መርሀ ግብሩ ይቀጥላል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በሥራ ሂደት ያጋጠማችሁ ፈተናዎች ካሉ ቢጠቅሱልኝ?

አቶ ሰለሞን፡- በሂደት እየተፈቱ መጥተዋል እንጂ ብዙ ችግሮች አጋጥመውናል፡፡ ባለፈው ዓመት አመራሮችም አሰልጥነን ወደ ምልመላ ልንገባ ስንል በጥልቅ ተሀድሶ ምክንያት ያሰለጥናቸው አመራሮች አብዛኛዎቹ ከሥልጣናቸው ተነስተዋል፡፡ ለምሳሌ አዳማ መቶ በመቶ ከከንቲባ እስከ ቀበሌ ሊቀመንበር ከሥልጣናቸው ሊነሱ ችለዋል፡፡ መቀሌም በተመሳሳይ፡፡ እናም አዲስ ለመጡት አመራሮች እንደገና መርሀ ግብሩን ለማስተዋወቅ ተገደናል፡፡

ሌላው ግዥ የሚፈፀመው የመንግሥትንና የዓለም ባንክን ሕግ በጠበቀና በአማከለ ሁኔታ ነው፡፡ ወደ ትግበራ ስንገባ በአካባቢ ልማት ለሚሰማሩ ሰዎች የተለያዩ የመሥሪያ ዕቃዎችን ገዝቶ በወቅቱ ማቅረብ ላይ ውስንነቶች አሉብን፡፡ በዚህ ዓመት ችግሩን ለመቅረፍ በየከተሞቹ የግዥ ባለሙያዎች ተቀጥረዋል፡፡ በተመሳሳይም ከምልመላ ጋር የተያያዙ ችግሮች አጋጥመውናል፡፡ ሆኖም እየፈታናቸው ሄደናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከተሞቹ ወደ ትግበራ ከገቡ ከአራት እስከ ስድስት ወር ሆኗቸዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለመርሀ ግብሩ ከተያዘው በጀት ውስጥ እስካሁን ምን ያህል ገንዘብ ወጪ ሆነ?

አቶ ሰለሞን፡- እስካሁን ድረስ ወደ ክልሎች የተላከው ለሥራ ማስፈፀሚያና ለተጠቃሚዎች የሚከፈል አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ተላልፎላቸዋል፡፡ ግን በርግጠኝነት ምን ያህሉን ተጠቀሙበት ወይም አልተጠቀሙበትም የሚለውን ሪፖርት ስላላደረጉልን እቅጩን መናገር አይቻልም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ሰለሞን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

 

ጌትነት ምህረቴ

 

Published in ኢኮኖሚ

ሳውዲ አረቢያ ላይ እስካሁን ቀጥተኛ ወታደራዊ ጥቃት ደርሶባት አሜሪካን ስትከላከልላት ባንመለከትም፣ ማንኛውም የጦር ከለላ የመስጠት የሁለትዮሽ ስምምነታቸው ግን እንዳለ ነው። በምላሹም ሳውዲም ቃሏን አክብራ የነዳጅ ዘይት ግብይቷን በዶላር ብቻ እየፈፀመች ትገኛለች። ስለዚህ አገራቱ ያሰሩት የወዳጅነት ውል እንደፀና ነው ማለት ነው። ከዚህ በኋላስ ግንኙነታቸው ወዴት ያመራ ይሆን? የሚለውን ጥያቄ የተለያዩ ምሁራን እና የዘርፉ ተንታኝኞች የተለያዩ ሀሳባቸውን ገልፀዋል፡፡

በቀደሙት ዓመታት ከዚህ መለስ የማይባል ጥቅምን ለአሜሪካን የሰጠውና፣ ለአሜሪካን ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ የበላይነት ጉልህ ድርሻ እንዳለው የሚነገረው ይህ ስምምነት፤ ለአሜሪካን የሚሰጠው ዋጋ በየጊዜው እየተመናመነ መምጣቱን የተለያዩ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። ይህንን ስምምነት አሜሪካን ብታፈርሰው የጉዳቷ መጠን ሲመዘን ከሳውዲ የበለጠ ነው ተብሏል። ምክንያቱም በሳውዲ በኩል ያለው የውል ግዴታ የነዳጅ ዘይቷን በአሜሪካን ዶላር ብቻ እንድትሸጥ የሚያደርግ ነው። ስለሆነም ስምምነቱ ቢፈርስ ሳውዲ ዘይቷን በፈለገችው የገንዘብ ዓይነት የመሸጥ ነፃነት ይሰጣታል። ይህ ደግሞ በአሜሪካን ላይ ምንም ያህል ጉዳት እንደማያስከትል የሚገልፁ አሉ።

የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት፣ «አሜሪካን ለሳውዲ እየሰጠች ባለው ወታደራዊ ከለላ ተጠቃሚ እየሆነች አይደለም፤ ስለዚህ፣ ሳውዲ ለአሜሪካን ክፍያ መፈፀም ይጠበቅባታል» ሲሉ ተናግረዋል። የፕሬዚዳንቱ ንግግር አሜሪካን ከሳውዲ ጋር ያሰረችውን ውል ባሻት ጊዜ ልታፈርሰው እንደምትችል የጠቆመ እንደሆነ እና ውሉ ለአሜሪካን አንገብጋቢ የሚሆንበት ዕድል እንዳበቃ ይጠቁማል። ይህ ማለት አሜሪካን ለሳውዲ ብላ ደሟን የምታፈስበት፣ አጥንቷን የምትከሰክስበት ምክንያት አይኖርም ማለት ነው። ስለዚህ የአሜሪካንና የሳውዲ ውል ሳውዲን ከሩሲያ ወታደራዊ ጥቃት የመታደግ አቅሙ የሳሳ መሆኑን የተለያዩ የዘርፉ ምሁራን ይገልፃሉ።

ሌላው ነጥብ ሩሲያ በመካከለኛው ምሥራቅ ለወጠነችው ዕቅድ ስኬታማነት ያላት ቁርጠኝነት ከፍተኛ ነው። ይኸው ቁርጠኝነቷ ከሳውዲ ጋር ቢያላትማት የሚገርም አይሆንም። ሳውዲ ለሶሪያና የመን ግጭቶች አንደኛዋና ዋነኛዋ የገንዘብ ምንጭ መሆኗን ሩሲያ ለረጅም ጊዚያት ስትወቅሰ እንደነበር የሚታወስ ነው። ይህንን በተመለከተ የኢራን ታዋቂ ዲፕሎማት የሆኑት ሰይድ ሁሤን ሞሳቪያን፣ «የሶሪያ ቀውስ፣ የሳውዲ ተቃዋሚዎችን በገንዘብና በመሣሪያ የመርዳት ውጤት ነው» በማለት የቀውሱን ቀጥተኛ ኃላፊነት ለሳውዲ አሸክመውታል።

ሩሲያም የዲፕሎማቱን አስተያየት ትጋራለች። ከብዙ ድካም በኋላ የተወሰኑ የሶሪያ ታጣቂዎች የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈራረሙ ሩሲያ ማድረግ ችላለች። ይሁንና፣ ከተኩስ አቁም ስምምነት አልፎ የሶሪያ ጦርነት ቢያበቃም እንኳን፤ ሳውዲ አረቢያና ኳታር እጃቸውን ከሶሪያ እስካላነሱ ድረስ ሶሪያ መረጋጋትን ታገኛለች ተብሎ አይታሰብም። ከእዚህ ቀደም ሳውዲ ከሶሪያ ጉዳይ ፊቷን እንድታዞር ለማግባባት ሩሲያ ያደረገችው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሁሉ ፍሬ ቢስ ሆኗል። በኢኮኖሚው መስክም ሳውዲ ሩሲያን ክፉኛ እየተፈታተናት ትገኛለች። ባጭሩ፣ ሳውዲ በሩሲያ ጎዳና ላይ መንገድ ዘግታ መቆሟ የሚታወስ ነው፡፡

እንደ አልጀዚራ የዜና ትንታኔ ከሆነም፤ ሳውዲን በአንዳች መንገድ ማስገደድ አስፈላጊ ስለሆነ ቀጥተኛ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ለሩሲያ ሁለተኛ የሌለው ብቸኛ አማራጭ ሆኗል። ለዚህ ደግሞ ቁርጠኝነቱም ብቃቱም አላት። ከቁርጠኝነቷ በተጨማሪም፣ ሩሲያ ሳውዲ ላይ አንዳች ቀጥተኛ ወታደራዊ ጥቃት ብትፈፅም አያሌ ጥቅሞችን የምታገኝ ይሆናል። ከእነዚህም ውስጥ ሳውዲ ከሶሪያና የመን እጇን እንድታነሳ በማስገደድ ሩሲያ በሁለቱ አገራት እንዲኖር የምትሻውን ሥርዓት ማምጣት ያስችላታል። በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ ያላትን ጉልበት በማሳየትም አካባቢው ላይ ያላትን ተፅዕኖ ታጠናክርበታለች። ኢኮኖሚዋን እየጎዳ ያለውን የነዳጅ ዘይት የዓለም ገበያ ዋጋም ከፍ ለማድረግ ይረዳታል። የተዘረዘሩት ነጥቦች፣ ሩሲያ ሳውዲ ላይ ወታደራዊ ጥቃት ብትሰነዝር ታገኛለች ተብሎ ከሚታሰቡት ጥቅሞች የተወሰኑት ሲሆኑ፤ በፖለቲካ መነጽር ሲታዩ ያላቸው ዋጋ የሩሲያን ቁርጠኝነት ያጠናክሩታል።

ለዚህ ትንታኔ ግብዓት የሆነው ሌላው ኩነት ደግሞ፣ 7 የሳውዲ ነገሥታትንና 12 የአሜሪካን ፕሬዚዳንቶችን የዘለቀው የአሜሪካንና የሳውዲ ፍቅር እየተቀዛቀዘ መምጣቱ፣ አሜሪካን ሳውዲን ከጥቃት ለመታደግ የሚኖራትን ተነሳሽነት እንደሚያሳንሰው መታመኑ ነው። ከ43 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የአሜሪካንና የሳውዲ ፍቅር አሁን ላይ ጋሬጣ በዝቶበታል። በይበልጥ አሜሪካን ላይ በደረሰው «9/11» በመባል ከሚታወቀው ጥቃት በኋላ ተባብሶበታል። ኦሳማ ቢንላዲን አቀናብሮታል ብላ አሜሪካን የምትወነጅለውና እ... መስከረም 11 ቀን 2001 በአሜሪካን ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ሲመረምር የሰነበተው የአሜሪካን መርማሪ ኮሚሽን፣ የምርመራው ውጤት ጣቱን ወደ ሳውዲ ቀስሯል። አሜሪካን በጥቃቱ ተሳትፈዋል ከምትላቸው 19 ተጠርጣሪዎች 15ቱ የሳውዲ ዜግነት ያላቸው ናቸው። በርግጥ ሳውዲ እንደአገር ከጥቃቱ ጋር ተያይዛ ባትጠቀስም፣ የጥቃቱ አቀናባሪዎች ኢኮኖሚያዊ መሠረታቸው ሳውዲ ውስጥ መሆኑን የምርመራ ውጤቱ ያጋልጣል።

«የሳውዲ ገንዘብ ሽብርተኝነትን እየደገፈ ነው» በሚል፣ አሜሪካ ሳውዲን በተዘዋዋሪ ኮንናለች። ይሁንና ሳውዲን በደፈናው ከመኮነን በዘለለ የአሜሪካን መንግሥት በጉዳዩ ላይ በይፋ ገፍቶ አልተጓዘበትም። እንዲሁም፣ ውጤቱን በይፋ ለሕዝብ ከመግለፅ ተቆጥቧል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የአሜሪካን መንግሥት በሳውዲ ላይ ያለው የጠበቀ ኢኮኖሚያዊና ስትራቴጂካዊ ፍላጎት ነው። ሆኖም፣ የአሜሪካን ኮንግረስ በሳውዲ ላይ የወታደራዊ መሣሪያ ሽያጭ ዕቀባ ለማድረግ ወይም ገደብ ለማበጀት ጉዳዩን እያጠናው ይገኛል፤ ይኸውም፣ የሁለቱን አገራት ፍቅር መቀዛቀዙን አመላካች ነው።

የተለያዩ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተንታኞች እንዳሉት በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2010 ጀምሮ ሳውዲ፣ የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስንና ኳታርን ተባባሪዎቿ በማድረግ ራሷን የቀጠናው ኃያል (Regional Power) የማድረግ እንቅስቃሴ እያደረገች ትገኛለች። በየመንና በሶሪያ የርስበርስ ግጭት ውስጥ እጇን በቀጥታ ከማስገባት ባለፈ፣ በቅርቡ ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ ወታደራዊ ካምፖችን መገንባት ጀምራለች (ኤርትራና ጅቡቲ በሂደት ላይ ነው)። የአክሲዮን ገበያውን ጨምሮ፣ በአሜሪካን ኢኮኖሚ ውስጥ ያላትን ከ750 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለማውጣት አሜሪካን ላይ ዛቻ እስከመሰንዘር ደርሳለች።

በተጨማሪም ፀረ አሜሪካንና ምዕራባውያን የሆኑ ኃይሎች የገንዘብ ምንጫቸው ሳውዲ ውስጥ ነው የሚለው ክስ ከየአቅጣጫው በርትቷል። አሜሪካን ከእነዚህ ኃይሎች የጥቃት ሥጋት ነፃ አይደለችም። ይኸውም፣ የአገራቱን ፍቅር አዳክሞታል። ከዚያም አልፎ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የነበራት ጂኦፖለቲካዊ ፍላጎት በተወሰነ መልኩ መቀየር ጀምሯል። በጦር መሣሪያ ግዢ ከዓለም አገራት 3ኛ ደረጃን የተጎናፀፈችው ሳውዲ፣ በዓመት 56 ቢሊዮን ዶላር ለዚሁ ዓላማ ታፈሳለች፤ ይኸውም የአሜሪካንን ኪስ የሚያደልብ ነው። ሳውዲ በአሜሪካን ኢኮኖሚ ውስጥ ያላት ከ750 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለአሜሪካን ኢኮኖሚ ትልቅ ሚና አለው፡፡

ሩሲያ በሳውዲ ላይ ጦርነት እንደማታውጅ ሁሉም የፖለቲካ ጠበብቶች ይስማማሉ። እነዚህ ጠበብቶች፣ «ምንም እንኳን ሩሲያ ሳውዲን ‹ውረጅ እንውረድ› በማለት ሠራዊቷን ልታዘምትባት ባትደፍርም፣ የተወሰኑ የሳውዲን ወታደራዊ ስትራቴጂክ ቦታዎች መርጣ በአየር ወይም በሚሳይል ልትደበድብ ትችላለች። ከሰፊ ጦርነት በመለስ ያለ አነስተኛ ወታደራዊ ጥቃት ብትፈፅም፣ ከአሜሪካንም ቢሆን ያን ያክል የከረረ ተቃውሞ አይገጥማትም» የሚል አስተያየት ያክላሉ። በርግጥ ይህንን ሃሣብ የሚያስጨብጡ ወቅታዊ ኩነቶች እየበረከቱ በመሄዳቸው፣ ከተቀሩት መላምቶች ይልቅ በፖለቲካ ልሂቃኑ ዘንድ ይኼኛው መላምት ሚዛን የደፋ ሆኗል። በእርግጥ፣ ይህም ቢሆን ያለአሜሪካን በጎ ፈቃድ አስቸጋሪ ነውና፣ ከድብደባው አሜሪካን አንዳች ጥቅም የምታገኝበት ሊሆን ይገባል። ከአሜሪካን አንፃር ካየነው፣ በርግጥ አሜሪካን ከሳውዲ ጋር ወደተካረረ ነገር መግባት አትፈልግም።

የሳውዲ ወቅታዊ ሁኔታ ለአሜሪካን ውለታ የገነነ ዋጋ የሚሰጥ አልሆነም። ስለዚህ፣ አሜሪካን ለሳውዲ ደኅንነት ያላትን ድርሻ ክብደቱን የምታሳይበት አጋጣሚ ትሻለች፤ በተቃራኒ ሳውዲ ከኢራን ጋር በብርቱ ተፋጥጣ ባለችበት በዚህ ወቅት ከሩሲያ ጋር መካረሯን ትታ ሰላም ለመፍጠር እየተጋች ትገኛለች፡፡

የሳውዲአረቢያው ንጉስ ሰልማን በሞስኮ የአራት ቀን ጉብኝት አድርገዋል፡፡ የንጉስ ሰልማን ይፋዊ ጉብኝትን ተከትሎ በሳውዲ ንጉሳዊ አስተዳደር እና በሞስኮ መካከል የተለየ የተባለለት 15 አዳዲስ ስምምነቶች ተፈርመዋል፡፡ በስምምነቱም ወቅት የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስርጌ ላቭሮቭ እንዳሉት፤ ስምምነቱ የአገሩቱን ግንኙነት ወደተለየ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ሳውዲ አረቢያም በበኩሏ ከሩስያ ኤስ 400 (S-400) የተሰኘውን የጦር መሳሪያ ልትገዛ እንደምትችል ጠቁማለች፡፡ እንደ የዘጋርዲያን ዘገባ ከሆነ አብዛኛው ስምምነት ሳውዲአረቢያ በተለያዩ የሀይል ምንጮች ላይ መዋለ ነዋይዋን እንድታፈስ የሚገብዝ ነው።

 

አብርሃም ተወልደ

 

Published in ዓለም አቀፍ
Wednesday, 11 October 2017 17:41

ፌዴራሊዝም እና ኢትዮጵያ

 

ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ የምርጫ ጉዳይ አይደለም። ብቸኛው አማራጭ ነው። የፌዴራል ሥርዓትን መከተል ለኢትዮጵያ እስትንፋስ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ጽንፈኛ የትምክህትና ጥበት ቡድኖች በኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት ላይ የሚሰጡትን አስተያየት ላዳመጠ ሳይደመም አይቀርም።

እነዚህ ቡድኖች ወይ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ አያውቁም፤ አሊያም ይህቺ አገር ቀጣይ እጣ ፋንታዋ ምንም ይሁን ምን ደንታ የላቸውም። ምክንያቱም በዛሬዋ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የፌዴራል ሥርዓቱን ለማፍረስ መዳዳት፣ የአገሪቱን ጉሮሮ ማነቅ፣ እስትንፋሷን መዝጋት፣ ሉዓላዊት አገርን መበታተን ብሎም ህዝብን ወደማያባራ ግጭት ውስጥ ማስገባት እንደሆነ መታወቅ አለበት።

የኢትዮጵያን ታሪክ የኋሊት መለስ ብሎ ላስተዋለ ሰው የሚረዳው ለረዥም ዓመታት በርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መዝለቋን ነው። በመላ አገሪቱ ተከስቶ ለነበረው የርስ በርስ ጦርነት እልባት የሰጠው የፌዴራል ሥርዓቱ ነው።

በኢትዮጵያ ዛሬ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ይዘዋል፤ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን መጠቀም ችለዋል፤ በማንነታቸው ኮርተዋል፤ አካባቢያቸውን በማልማት ከምጣኔ ሀብታዊ ዘርፉ ተጠቃሚ ሆነዋል። ይህን የህዝቦችን መብት ያስጠበቀ ሥርዓት ለማፍረስ መንቀሳቀስ መዘዙ የከፋ ነው። ኢትዮጵያ ባለፉት 26 ዓመታት ፌዴራላዊ ሥርዓትን መከተል ችላለች። ዜጎች ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ተጠቃሚነታቸውን አረጋግጠዋል።

ፌዴራሊዝም ወይም ፌዴራላዊ ሥርዓት ምንድነው? ፌዴራላዊ ሥርዓት ማለት ሁለት ወይም ከሁለት በላይ መንግሥታት (ፌዴራልና ክልል መንግሥታት) የሚፈጥሩት የራስ አስተዳደርና የጋራ አስተዳደርን ያጣመረ፣ በቃል ኪዳን የሚመሠረትና የሚመራ አጋርነት ነው፡፡ ይህ አጋርነት በመካከላቸው ሊኖር የሚገባውን የሥልጣን ክፍፍልና ዝምድና ይወስናል፡፡ አንዱ የሌላውን ቅንነትና አብሮ የመኖር እሳቤን በማመን ላይ የተመሠረተ፤ አንዱ የሌላውን ልዩ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ኃይማኖት በማክበርና በዕኩልነት በመጠበቅ ላይ የተመሠረተ ሥርዓት ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን 28 የሚደርሱ አገራት በፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥት የሚተዳደሩ ናቸው። 40 በመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብ በእነዚህ አገራት ሥር የሚኖሩ መሆኑም በፌዴራሊዝም ዙሪያ ጥናት ያካሄዱ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። ዴሞክራሲን ለማስፈን ፌዴራል ሥርዓት ከሌሎች የመንግሥት አወቃቀር መልኮች የበለጠ የተሻለ በመሆኑ 21ኛው ክፍለ ዘመን አገራት ወደ ፌዴራሊዝም አስተዳደር የሚሸጋገሩበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

አገራት ፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥትን ምርጫቸው የሚያደርጉበት የተለያዩ ምክንያቶች አሏቸው። አራት ዋና ዋና ምክንያቶችም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከዚህም ውስጥ አንዱ ብዝሃነትን ማስተናገድ፤ ሁለተኛው ደግሞ ሰፊ ገበያና ትልቅ ኢኮኖሚ የመገንባት ፍላጎት ነው። ሦስተኛው ምክንያት ጠንካራ የመከላከያ ኃይልና የደህንነት ሥርዓት ባለቤት መሆን ነው፡፡ አራተኛው ምክንያት አስተዳደራዊ አመቺነትን መፍጠር ነው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች መካከል ኢትዮጵያን የፌዴራል ሥርዓትን እንድትከተል ያስገደዳት በአገሪቱ ያለው ብዝሃነት ነው።

የኢፌዴሪን ሕገ መንግሥት መሠረታዊ ዓላማዎች በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ በዚህ መልኩ ሰፍሯል። በአገራችን ባለፉት ሥርዓቶች ይስተዋሉ የነበሩት የተዛባ ግንኙነቶችን ለማስተካከል፣ ቀድሞ ያላቸውን የጋራ አብነቶችና እሴቶች ትስስር ለማጠናከር፣ ዘላቂ ሠላምን፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ለማስፈን፣ የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት ቃል የገቡ መሆናቸውን፣ ይህን ለማሳካት የግለሰብም ሆነ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ህዝቦች መብቶችና የፆታ ዕኩልነት ማረጋገጥ፣ ባህሎችና ኃይማኖቶች ያለ አድሎና ልዩነት እንዲራመዱ ማድረግ ፅኑ ዕምነታቸው እንደሆነ መወሰናቸውን የሚል ነው፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ሁሉን ያሟላ ዘመናዊ የሚባል ሕገ መንግሥት ነው። የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በየዘርፉ ማለትም በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የህዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያደርግ አንቀፆችን አካቷል። በዚህ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ደጋግሜ መጠቃቀሴን ለማስታወስ እወዳለሁ።

ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ የአስተዳደር ሥርዓትን የምትከተል አገር ነች። አገሪቱ በዚህ ሥርዓት መተዳደር ከጀመረች ወዲህ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችላለች። ፌዴራል ሥርዓት ከሌሎች ሥርዓቶች የሚለይባቸው አምስት መሠረታዊ የተባሉ ባህሪያት አሉት፡፡ የመጀመሪያው የመንግሥት አወቃቀርና ተጠያቂነት ማስፈን ነው። ሁሉም ፌዴራል አገሮች ቢያንስ ሁለት መንግሥታት (ፌዴራልና ክልሎች) አሏቸው፡፡ እነዚህ መንግሥታት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው፣ ተጠያቂነታቸውም ለመረጣቸው ህዝብ ነው፡፡ እነዚህ መንግሥታት ህልውናቸው የሚረጋገጠው በሕገ መንግሥት ነው፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱ አወቃቀር እንደየአገራቱ ሁኔታ ጂኦግራፊያዊ ወይም በማንነት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለመረጣቸው ህዝብ ነው፡፡ ፌዴራል መንግሥት የሚመረጠው በአጠቃላይ በአገሪቱ ህዝብ ነው። የክልል መንግሥታት ደግሞ በየክልሉ ውስጥ በሚኖሩ ህዝቦች ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት በዋናነት የተዋቀረው በህዝቦች ማንነት ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ይህ የመንግሥት አደረጃጀት የተመረጠበት ምክንያት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባለፈው ታሪክ የተነፈጉትን መብት፣ ታፍኖ የነበረውን ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህልንና ሌሎች የማንነት መገለጫዎችን በሕገ መንግሥት ዋስትና እንዲያገኙና በተግባርም ተፈፃሚ ማድረግ የሚያስችል አወቃቀር ስለሆነ ነው፡፡

እነዚህ ህዝቦች የተዛባው ግንኙነት መወገዱን ማረጋገጫ መሣሪያ እንደሆነ ስላመኑበትና በዚህ አወቃቀር አዲስ የዕኩልነት ግንኙነትና የጋራ ህልውና እንዲመሠረት ስለወሰኑ የተከተሉት አወቃቀር ነው፡፡ የአገራችን የአከላለል መሥፈርት ማንነትን፣ ቋንቋን፣ አሠፋፈርንና ፈቃደኝነትን ታሳቢ ያደረገው በአገሪቱ ህዝቦች የትግል ታሪክ የዕኩልነት ጥያቄ መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ነው። የማንነት መገለጫ የሆኑትን ራስን በራስ የማስተዳደር፣ ቋንቋን፣ ባህልንና ታሪክን ለማጥናት ለመንከባከብና ለማሳደግ ብቸኛ አማራጭ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡

ሁለተኛው የፌዴራላዊ ሥርዓት ባህሪ የሆነው የሥልጣን ክፍፍል ማለትም የራስ አስተዳደር እና የጋራ አስተዳደር መመሥረት መቻል ነው። የሥልጣን ክፍፍል የፌዴራል ሥርዓት ዋነኛ መገለጫ ነው፡፡ እያንዳንዱ መንግሥት በተሰጠው አስተዳደራዊ ወሰን ውስጥ ሕግ የማውጣት፣ ሕግ የመፈፀም፣ ሕግ የመተርጎምና ገቢን የመሰብሰብ ሥልጣን አለው፡፡ የሥልጣን ክፍፍሉ እንደየአገራቱ ሁኔታ ቢለያይም አገራዊ ጉዳዮችንና አንድነትን ለማስጠበቅ ጠቀሜታ ያላቸው ሥልጣኖች ለፌዴራሉ መንግሥት የሚሰጡ ናቸው። ከክልሎችና ብሄር ብሄረ-ሰቦች ልዩ ሁኔታና ባህል ጋር የተያያዙ ሥልጣኖች ደግሞ ለክልሎች ይሰጣሉ፡፡ በኢትዮጵያም ፌዴራል መንግሥትና ክልሎች ሕግን የማውጣት፣ ሕግን የመፈፀምና ሕግን የመተርጎም ሥልጣን አላቸው፡፡ የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን በአንቀፅ 51 የክልሎች ደግሞ በአንቀፅ 52 ተዘርዝሮ ይገኛል፡፡ ተለይተው ያልተዘረዘሩ ቀሪ ሥልጣኖችም ለክልሎች ተሰጥተዋል፡፡

ሦስተኛው የፌዴራል መንግሥታት ባህሪ የሆነው ሁሉም ፌዴራል አገሮች የተፃፈ ሕገ መንግሥት ያላቸው መሆኑ ነው። ሕገ መንግሥት የስምምነታቸው ወይም ቃል ኪዳናቸው ማሰሪያ ሰነድ ነው፡፡ በአንድ በኩል አንዱ እርከን ሥልጣኑን ተግባራዊ በሚያደርግበት ወቅት የሌላውን እርከን ሥልጣን እንዳይነካ የሚገታው ወይም ሥልጣኔ ተነካ የሚል ካለ ተጠቃሽ ሆኖ የሚያገለግል የተፃፈ ህገ መንግሥት መኖር የግድ ይሆናል፡፡ እንደየአገራቱ ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ሥርዓት ቢለያይም ሁሉም ፌዴራል አገሮች የሕገ መንግሥታቸውን የተወሰኑ አንቀፆች ያለፌዴራል መንግሥትና ክልሎች ስምምነት ሊያሻሽሉ አይችሉም፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችና የኅብረተሰብ ተወካዮች የድርድር ውጤት ነው፡፡

አራተኛው የፌዴራል ሥርዓቶች ባህሪ የሆነው ሁሉም ፌዴሬሽኖች ሁለት ምክር ቤቶች አሏቸው፡፡ አንዱ "የተወካዮች ምክር ቤት" ወይም "የታችኛው ምክር ቤት" የሚባል ነው። ሌላው ደግሞ "የላይኛው ምክር ቤት" ወይም "ሁለተኛ ምክር ቤት" በሚል ይታወቃል፡፡ ሁለተኛው ምክር ቤት በተለያዩ ፌዴራል አገራት የተለያየ መጠሪያ አለው። በኢትዮጵያም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተብሎ ይጠራል፡፡ አወቃቀርና ሥልጣኑም እንደየአገራቱ ሁኔታ ይለያያል። የኢትዮጵያ ለእያንዳንዱ ብሄር፣ ብሄረሰብ ወይም ህዝብ አንድ ውክልና ለተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ተጨማሪ አንድ ወኪል እንዲኖር ያደርጋል፡፡

የምክር ቤቱ ተወካዮች አመራረጥን በተመለከተ በአንዳንድ ፌዴሬሽኖች በቀጥታ በህዝብ ሲመረጡ በሌሎች ደግሞ ከግማሽ በላይ ወይም ከግማሽ በታች ተወካዮች በክልሎች ሥራ አስፈፃሚዎች ይመረጣሉ፡፡ በኢትዮጵያ አባላቱ በክልል ምክር ቤቶች ይመረጣሉ ወይም ምክር ቤቶቹ በክልሎች ህዝቦች በቀጥታ እንዲመረጡ ማድረግ ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የጋራ ገቢዎች የሚከፋፈሉበት መንገድ ይወስናል፣ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠውን ድጎማ ቀመር በማውጣት ያከፋፍላል፣ ሕገ መንግሥትን ይተረጉማል፣ በክልሎች መካከል አለመግባባት ሲፈጠር መፍትሄ ይሰጣል፡፡

አምስተኛው የፌዴራል ሥርዓት ባህሪያት የሆነው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ገላጋይ ተቋም መኖር ነው። የፌዴሬሽኖች ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ክፍፍል ጥቅል፣ መደራረብና መጋራት የሚታይበት ነው፡፡ በመሆኑም በአፈፃፀም ሂደት አንዱ የሌላውን ሥልጣን ሊነካ ስለሚችል በዚህ ጊዜ የሚነሳን አለመግባበት በውይይት መፍታት ካልተቻለ የዳኝነት ፍርድ የሚሰጥ ገላጋይ ተቋም አላቸው፡፡ በዚህ ዙሪያም እንደየአገሩ ልዩነቶች አሉ፡፡ በኢትየጵያ ሕገ መንግሥታዊ አለመግባባቶችን ግልግል የሚሰጠው ተቋም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡

ኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት መከተል ከጀመረች ጊዜ አንስቶ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችላለች። ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነታቸውንና ነፃነታቸውን በማረጋገጣቸው በአገሪቱ ዘላቂ ሠላም ሰፍኗል። በዚህም ፈጣን ልማት አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይህን ጥቅም ያስገኘላቸውን ሥርዓት መነካካት ወይም ለማፍረስ መሞከር የማይታሰብ ነው። በመሆኑም በሁለቱም በኩል ማለትም በትምክህትም ሆነ በጥበት የምናስተውላቸውን ጽንፈኛ ኃይሎች መዋጋት የሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ግዴታ ነው። ትምክህትና ጥበት የፌዴራል ሥርዓታችን ጠንቆች መሆናቸውን ተገንዝበን የሃሳብ ትግል ልናደርግባቸው ይገባል።

 

ወንድይራድ ሀብተየስ

 

 

 

 

 

Published in አጀንዳ

 

በኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት ከተጀመረ ከመቶ ዓመት በላይ ቢያስቆጥርም ከአገሪቷ የባንክ ታሪክ አንፃር ተነስተን ስንመለከተው ግን የባንክ አብዮት ተካሄደ የምንለው ከደርግ ሥርዓት ውድቀት በኋላ ያለውን ነው። ይህ ዝም ብሎ የሚባል ሳይሆን የዘርፉን ታሪክ መለስ ብሎ ለሚመለከት በቀላሉ የሚረዳው ሀቅ ነው። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ብቻ የባንኩ ዘርፍ አስደማሚ በሆነ ፍጥነት እያደገ መጥቷል። ይህንን የዕድገት ጉዞ ከጎረቤት አገራትም ይሁን ከተቀሩት አፍሪካውያን አገራት ጋር ስናነፃፅር ብዙም የሚያስመካ እንዳይደለ እንረዳለን። ዕድገቱ ተደራሽነትን በሚፈለገው ልክ አላረጋገጠምና።

ያም ሆኖ ታዲያ የኢትዮጵያ የባንክና የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት የቁጠባ ሂሳብ ቁጥር 43 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ደርሷል፤ አንድ ሺህ 748 የባንክ ቅርንጫፎች ተከፍተዋል፤ የክፍያ መፈፀሚያ ነቁጦች ቁጥር 492፤ የኢ ቲ ኤም ማሽኖች ቁጥር ደግሞ ሁለት ሺህ 743 ደርሷል። የወኪል ባንክ ቁጥርም ዕድገት አሳይቶ 10 ሺህ 481 ሆኗል። በዚህ መልክ የተስፋፋው የባንክ አገልግሎት የቁጠባ መጠኑን ወደ 568 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር አድርሶታል። የብድር መጠኑም 560 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ደርሷል።

የአገሪቷ የባንክ አገልግሎት ከነችግሩም ቢሆን የተጠቀሰውን ያህል ዕድገት አስመዝግቧል። ይህ ዕድገት በአንድ ጀምበር የመጣ አይደለም። ይልቁንም በጥብቅ የማይክሮ ፋይናንስ ፖሊሲና አፈፃፀም እንጂ። ስለሆነም የመንግሥት ቁርጠኛ አፈፃፀምና አገር በቀል ፖሊሲ ዘርፉን እዚህ አድርሶታል። በተጓዳኝም ዕያደገ ያለው ኢኮኖሚና የህዝብ ቁጥር እጅግ የተቀላጠፈና ዘመናዊ ብሎም ተደራሽ የባንክ አገልግሎት የሚፈልግበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

መንግሥትም ይህ ዕድገት እንዳለ ይጠቅስና ተደራሽነቱ ገና ዝቅተኛ ነው የሚል ግምግማ አለው። ተደራሽነትን ይበልጥ ለማስፋፋትም የተቀመረ ስትራቴጂን ይዞ ብቅ ብሏል። ይህ ስትራቴጂ የባንክ አገልግሎትን በብዛትና በጥራት ለማድረስ ሁነኛ መፍትሄ እንደሆነ ተገልጿል።

አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ሁለት መከራከሪያዎችን ይዘው ብቅ ብለዋል። በአነድ ወገን ያሉቱ አሁን ያለንበት ዘመን ቴክኖሎጂን በብዛትና በጥራት የሚፈልግ መሆኑን በመጥቀስ ቅርንጫፎችን ከማስፋፋት ይልቅ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶችን ማስፋፋት ይበጃል ይላሉ። ይህንን ሀሳብ የሚያነሱ ምሁራን መከራከሪያ ነጥባቸው አሁን በአገሪቱ ያለው አብዛኛው ህዝብ ወጣት እንደመሆኑ ለቴክኖሎጂ ቅርብ ነው፤ ቴክኖሎጂው ደግሞ በብዛትና በጥራት እየተስፋፋ መጥቷል፤ ስለሆነም የግድ ወደ ባንኮች ቅርንጫፍ መሄድ ስለማይገባ ሁሉም በየቤቱ አገልግሎቱን የሚያገኝበትን ዕድል መፍጠር ይቻላል የሚል ነው።

ዛሬ እስከ 50 ሚሊዮን የሚደርስ የሞባይል ተጠቃሚ አለ። ኢትዮ ቴሌኮም ደግሞ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የተጠቃሚውን ቁጥር 100 ሚሊዮን አደርሳለሁ ብሎ ታትሮ እየሠራ ነው። ስለሆነም ይህንን ያህል ህዝብ በቀላሉ ማግኘት የሚቻለው በሞባይል ባንኪንግ ነው ይላሉ። በቅርንጫፍ ለመድረስ መሞከር አክሳሪ ባይሆንም በሚፈለገው ልክ ግን አትራፊ እንደማያደርግ ይገልፃሉ። የሞባይል፣ የኢንተርኔትና የወኪል የባንክ አገልግሎቶች በመስጠት ብቻ 70 እና 80 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቷን ህዝብ ለባንክ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ይቻላልም ሲሉ ይከራከራሉ።

በሌላ ወገን ደግሞ ከቴክኖሎጂው ይልቅ ቅርንጫፎችን ማስፋፋት አዋጭ ነው ብለው የሚከራከሩ አልታጡም። የእነዚህ ምሁራን እይታ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የአገሪቷ ህዝብ የሚኖረው በገጠር እንደመሆኑና ጥቂት የማይባለው ጎልማሳም ለቴክኖሎጂ ባዳ በመሆኑ አዋጭው መንገድ ቅርንጫፍን ማስፋፋት ነው የሚል ነው። ይህ ማለት ግን ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት አያዋጣም ማለት እንዳልሆነ በመግለፅም ዋናው ትኩረት መሆን ያለበት ግን ቅርንጫፎች ላይ ነው ባይ ናቸው።

ዛሬም ድረስ በሰለጠኑት አገራት ሳይቀር የባንክ ቅርንጫፎችን መክፈት እንዳለ መሆኑን በመግለፅም በኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ፊትን ወደ ቴክኖሎጂ ማዞር አዋጭም ተመራጭም አይደለም የሚል ሙያዊ አተያይ አላቸው።

የሁለቱም ወገኖች ምሁራዊ ዕይታ መንግሥት ይዞት ከመጣው ስትራቴጂ አንፃር የሚነቀፍም ሆነ የሚጣል አይደለም። ሁለቱም ያስፈልጋሉ፤ ሁለቱም ጊዜው የሚጠይቀው አማራጮች ናቸው። በዚህም ምክንያት ጭምር መንግሥት ስትራቴጂውን በዚህ አግባብ ቃኝቶ ማውጣቱ በእርግጥም ተገቢ ነው። ስለሆነም ባንኮች እንደሚገቡበት አካባቢ ተጨባጭ ሁኔታ እያዩና እየመዘኑ አዋጭ የሚሉትን አማራጭ ተግባራዊ ማድረግ ይገባቸዋል። ቴክኖሎጂው በደረሰበት መንደር የቴክኖሎጂ አማራጮችን፤ ባልደረሰበት ደግሞ ቅርንጫፎችን እያስፋፉ መሄዱ እንደ አገር ተጠቃሚ ያደርጋልና።

መንግሥትም ያሉበትን እንደ መብራትና ስልክ ያሉ የመሰረተ ልማት ሥራዎቹን በጊዜና በፍጥነት ማዳረስ አለበት። ከዚህ ጎን ለጎንም በየአምስት ዓመቱ እያንዳንዱ የንግድ ባንክ ሊደርስ የሚገባበትን ደረጃ እንደየወቅቱ እየከለሰና እያስገደደም ጭምር ዘርፉን በዋና ባለቤትነት እየተቆጣጠረ መቀጠል አለበት እንላለን።

 

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ

 

የፌዴራል ፖሊስ በሦስት ግለሰቦች የተመዘበሩ 100 ጥንታዊ የብራና መጻሕፍትን አስመልሶ በቅርስነት እንዲቀመጡ ለቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አስረከበ።

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የልዩልዩ ወንጀል ምርመራ ዲቪዥን ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ሞላ ናደው በርክክብ ሥነሥርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ አሁን ከተያዙት መካከል ብዛቱን የያዙት ከቅርሶቹ ጋር ተመሳስለው በመሰራጨትና በመሸጥ ላይ የተገኙ ናቸው። በተለይ በአንዱ ዘራፊ የተገኘው የብራና መጻሕፍት መነሻው የስጦታ እቃ ሽያጭ ነው። በሱቁ፣ በቤቱና በሌሎች ቦታዎች ውስጥ ደብቆ ሽፋኑን የስጦታ እቃ መሸጫ አድርጎ ነው የተያዘው።

እንደ ኢንስፔክተሩ ገለጻ፤ ማህበረሰቡ በሰጠው ጥቆማ መሰረት የግለሰቡ ቤትና ሱቁ ሲፈተሽ 65 የብራና መጻሕፍት ተገኝተውበታል። ይሄው ግለሰብ እንደ ዝሆን ጥርስና ሌሎች በቅርስነት የሚወሰዱ ነገሮችንም ለንግድ ማቅረቡ ተደርሶበታል። በዚህ ወንጀልም ግለሰቡና ሌሎች ሁለት ሰዎች በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል።

የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የቅርስ አጠባበቅ አዋጅ 209 አንቀጽ 8 መሰረት የብራና መጻሕፍት ቅርስ ናቸው። ቅርስ ደግሞ በአገሪቱ ህግ በምንም መልኩ ከአገር ወጥቶ ሊዘዋወርና ወደ ሌላ ወገን ሊሸጋገር አይችልም። ይሁን እንጂ በየጊዜው እየተወሰዱና እየተዘረፉ ያሉት የብራና መጻሕፍት ቁጥር ስፍር የላቸውም። በሌሎች አገራትም በሙዚዬም ደረጃ ተቀምጠውና በማይሆኑ ሰዎች እጅ ላይ ወድቀው የሚታዩት ብዙ ናቸው።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ አሁን ላይ ልክ እንደ አደንዛዥ ዕጽ በድብቅ እየተሸጡ ያሉት የብራና መጻሕፍትን ስርቆት ለማስቀረት ለሚመለከታቸው አካላት በቅርስ ዙሪያ ስልጠና እየተሰጠ ነው። ነገር ግን ይህ ብቻ በቂ ስላልሆነ የእያንዳንዱ ዜጋ ጥቆማና ቁርጠኝነት ሊኖር ይገባል። በየደረጃው ያለው አካል ለቅርሶች ሁለንተናዊ ጥበቃ የበኩሉን ሊያበረክት ይገባል።

በባለስልጣኑ የቅርስ ጥበቃና ምዝገባ ቁጥጥርና ደረጃ ማውጣት ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ አበባው በበኩላቸው፤ በሦስት ግለሰቦች ብቻ ይህን ያህል መጽሐፍ መዘረፉ የችግሩን ስፋት ያሳያል። ስለሆነም በተለይም የቅርሶቹ ባለቤት የሆኑት የእምነት ተቋማት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና ሁሉም ዜጋ ለጉዳዩ ትኩረት ሊቸረው ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከአምስት መቶ ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ የብራና መጻሕፍት ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል፤ ከእነዚህም መካከል ደግሞ ብዙዎቹ የሚገኙት በየቤተ እምነቱ መሆኑም ተጠቁሟል።

 

ጽጌረዳ ጫንያለው

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።