Items filtered by date: Monday, 02 October 2017
Monday, 02 October 2017 23:48

ማረፊያ ያጣው ቻን ዋንጫ

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በጥር 2018 የሚስተናገደውን የአፍሪካ አገራት ቻምፒዮን ሺፕ (ቻን) የአዘጋጅነት መብትን ከኬንያ ላይ መንጠቁ ይታወሳል፡፡ ኬንያ ውድድሩን ለማስተናገድ ያልተሳካ ጥረት ማድረጓን ተከትሎ የካፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጋና ርዕሰ መዲና አክራ ከሳምንት በፊት ባደረገው ስብሰባ የምስራቅ አፍሪካዋ አገር ውድድሩን እንድታዘጋጅ ወስኗል፡፡

ኬንያ በ2018 ውድድሩን ለማስተናገድ ተመርጣ የነበረ ቢሆንም ውድድሩን ለማስተናገድ የሚያስፈልጉ ስታዲየሞች ጥገና ግን እስካሁን ድረስ ማለቅ አለመቻላቸው የቻን ዋንጫን እንዳታዘጋጅ አግዷታል፡፡ ከወር በፊት የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአገሪቱ በቅርብ የተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በስልጣን ላይ ያሉት ኡሁሩ ኬንያታ ተቀናቃኛቸውን ራይላ ኦዲንጋን በልጠው አሸንፈዋል ያለውን የኬንያ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሽሮ ዳግም አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ መወሰኑ መንግሥት ፊቱን ወደ ምርጫው እንዲያዟር አድርጎታል፡፡ ይህንን ተከትሎም መንግሥት ለቻን ውድድር መስተንግዶ የሰጠው ትኩረት አነስተኛ ሆኗል። ኬንያ ውድድሩን በናይሮቢ፣ ማቻኮስና ሞምባሳ በሚገኙ አምስት ስታዲየሞች ለማስተናገድ አቅዳ የነበረ ሲሆን ከአምስቱ ስታዲየሞች ሁለቱ ብቻ በተሻለ ይዞታ ላይ ይገኛሉ፡፡

ካፍ ውድድሩን በኬንያ ፋንታ እንዲያዘጋጅ የመረጠው አገር በይፋ ባይታወቅም ከሞሮኮ፣ ዛምቢያና ደቡብ አፍሪካ አንዱ ውድድሩን የማስተናገድ መብት ሊሰጠው እንደሚችል እየተጠበቀ ይገኛል። ኢትዮጵያም ይህን ውድድር ለማዘጋጀት አነስተኛ ቢሆንም ዕድሉ ሊሰጣት እንደሚችል ተገምቷል። ከ21 ዓመታት በፊት ኬንያ የ1996ቱን የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ የነበረች ቢሆንም ልክ እንደአሁኑ ዝግጅት ላይ ደክመት ማሳየቷን ተከትሎ ዕድሉ ለደቡብ አፍሪካ ተሰጥቷል፡፡

ውድድር ለማስተናገድ በተቃረበበት ወቅት ዘወትር ፈተና ሲገጥመው የሚስተዋለው ካፍ የ2015 አፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ጥቂት ቀናት ሲቀረው በኢቦላ ወረርሽኝ ምክንያት አዘጋጇ ሞሮኮ አሻፈረኝ በማለቷ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ይታወሳል። በዚህም ሞሮኮ ከውድድር ታግዳ መቶ ሺ ዶላር ቅጣት ተላልፎባት ነበር። ይሁን እንጂ በወቅቱ የለብለብ ቢሆንም ባልተጠናቀቁ ስታድየሞቿ ጋቦን ውድድሩን አዘጋጅታ ካፍን መታደግ ችላለች።

ካፍ ከኬንያ የነጠቀውን የቻን አዘጋጅነት መብት ለሌላ አገር በቀናት ውስጥ እንደሚሰጥ ቢጠበቅም ከሳምንት በላይ አዲስ ነገር ማየት አልተቻለም። ይህም የቻን ውድድር እንደ አፍሪካ ዋንጫ ብዙ እውቅናና ዝና ከማጣቱ ጋር ተያይዞ አገራት የማዘጋጀት ፍላጎታቸው አነስተኛ በመሆኑ ሳይሆን እንዳልቀረ እየተነገረ ይገኛል።

በዕድሜ ትንሹና የአገር ውስጥ ሊጎች ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የቻን ዋንጫ እስካሁን ማረፊያ አለማግኘቱ ብቻም ሳይሆን ውድድሩን ለማዘጋጀት ብቁ ባልሆነ አገር ላይ ያርፋል የሚል ስጋት በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ አድሯል። ካፍም ከሦስት ወር ያነሰ ጊዜ የቀረውን ውድድር እልባት ከመስጠት ይልቅ ዝምታን መርጧል። ኢንሳይድ ወርልድ ፉትቦል በድረ ገፁ ሰሞኑን እንዳስነበበው ሞሮኮ ያመለጣትን የ2015 አፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነት በቻን ለማካካስ ፍላጎት አሳይታለች። ለዚህም በቂ መሰረተ ልማትና የማዘጋጀት አቅም ስላላት ከሌሎች አገራት የተሻለ ዕድሉን ልታገኝ ትችላለች። ከዚህ ባሻገር የሞሮኮው እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፋውዚ ሌክጃ የአዲሱ የካፍ ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ ደጋፊና የካፍ ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ መኖራቸው አዘጋጅነቱን በሞሮኮ ላይ ተስፋ እንዲጣል አድርጓል።

አንጎላ፤ ቡርኪናፋሶ፤ ካሜሩን፤ ኮንጎ፤ ኢኳቶሪያል ጊኒ፤ ኮትዲቯር፤ ሊቢያ፤ ሞሪታኒያ፤ ሞሮኮ፤ ናሚቢያ፤ ናይጄሪያ፤ ሱዳን፤ ኡጋንዳና ዛምቢያ በዚህ ውድድር ለመካፈል ማጣሪያውን አልፈው ውድድሩን በጉጉት እየጠበቁ የሚገኙ አገራት መሆናቸው ይታወቃል።

 

ቦጋለ አበበ

Published in ስፖርት

ጉዬ አዶላ

 

ከሳምንት በፊት በተካሄደው የበርሊን ማራቶን ቀጣዩን የዓለም ክብረወሰን ማን እንደሚያሻሽለው በጉጉት የመጠበቅ ምክንያት የአትሌቲክስ አፍቃሪው ትኩረት በታላላቆቹ አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለ፣ ዊልሰን ኪፕሳንግና ኢሉድ ኪፕቾጌ ላይ አርፎ ነበር። ውድድሩ ላይ የታየው ግን ለክብረወሰን የታሰቡት ቀነኒሳ በቀለና ዊልሰን ኪፕሳንግ አቋርጠው ሲወጡ ያልታሰበው ወጣት ኢትዮጵያዊ አትሌት ጉዬ አዶላ ያልተጠበቀ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።

ጉዬ እንኳን የማሸነፍ ግምት ሊሰጠው ይቅርና የማራቶን ውድድር ላይ ተወዳድሮ አያውቅም። በዚህ በበርሊን ማራቶን እንደሚወዳደር ያወቀውም ውድድሩ አራት ቀናት ሲቀሩት ነበር። ውድድሩ ሲያልቅ ግን ብዙዎች አድናቆታቸውን ከመግለፅ ባለፈ መወያያ አድርገውታል። ጉዬ አዶላ እስከመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ እልህ በሚያስጨርስ ሁኔታ ተፎካክሮ በጥቂት ሰከንዶች በኢሉድ ኪፕቾጌ ተበልጦ ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል። ያስመዘገበውም ሰዓት በርቀቱ ከቀነኒሳ ቀጥሎ በዓለም ሦስተኛው ፈጣን ሰዓት ሆኗል። ለመጀመሪያ ጊዜ ማራቶንን በሮጠ አትሌት የተመዘገበ የዓለም ክብረወሰን ሆኖም ተመዝግቧል።

የሃያ ስድስት ዓመቱ ጉዬ አዶላ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ቢሉ በምትባል አካባቢ የተወለደ ሲሆን፣ እንደ ቀደሙት አትሌቶች ሩጫን የጀመረው በህፃንነቱ ትምህርት ቤት በነበረበት ወቅት ነው። ዕድሜው 17 ሲሞላ ለቀጣይ ስልጠናዎች አዲስ አበባ በመምጣት የአምቦ አትሌቲክስ ክለብ አሰልጣኝ የሆኑት አቶ ተፈሪ መኮንን በሩጫ ህይወቱ ላይ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ መረጃዎች ያመለክታሉ። የሩጫ ህይወቱ ማንሰራራት የጀመረው ግን በኦሮሚያ የውሃ ሥራዎች ክለብ ቆይታው ነበር።

የመጀመሪያው ትልቅ ውድድር የነበረው ከሦስት ዓመታት በፊት ማራኬሽ ከተማ በተደረገው የግማሽ ማራቶን ውድድር ነው። ይህም ለቀጣይ ውድድሮቹ ፈር የቀደደለት ሲሆን፤ በዚያው ዓመትም በተመሳሳይ ርቀት እንዲሁም በ10 ኪሎ ሜትር ብዙ ውድድሮችን አድርጓል። ነገር ግን ብዙ የሚያስደስት ውጤት ማምጣት አልቻለም። ምንም እንኳን በአሰልጣኞቹ አስተያየት ማራቶን ላይ እንዲሳተፍ ምክር ቢሰጠውም ጉዬ ለማራቶን ሩጫ ምንም ፍላጎት አልነበረውም። አሁን ግን ያለምንም ጥርጣሬ የማራቶን ሯጭ ነው። በበርሊን ያጠናቀቀበት ሰዓት ከዓለም ክብረወሰኖች በ49 ሰከንዶች ብቻ የዘገየ ሲሆን በቀጣይ ኢትዮጵያ በማራቶን ተስፋ ከምትጥልባቸው አትሌቶች አንዱ ለመሆን ችሏል።

 

ቦጋለ አበበ

Published in ስፖርት

አልማዝ አያና በውድድር ዓመቱ የአምስት ሺ ሜትር ክብረወሰን እንደምታሻሽል ይጠበቃል፤

 

2009 የውድድር ዓመት በአትሌቲክሱ ዓለም የተለያዩ የዓለም ክብረወሰኖች ተሻሽለው የ2010 የውድድር ዓመት የአትሌቲክስ ፉክክሮች ከየአቅጣጫው የሚፋፋምበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ከለንደን የዓለም ቻምፒዮና መልስ በርካታ የዓለማችን ኮከብ አትሌቶች በቂ እረፍት ወስደው በውድድር ዓመቱ ወደ ፉክክር ለመግባት ዝግጅት በማድረግ ተጠምደዋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥም ከአጭር ርቀት አንስቶ በሜዳ ተግባራትና ረጅም ርቀት ውድድሮች በውድድር ዓመቱ በርካታ የዓለም ክብረወሰኖች ይሻሻላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህ የውድድር ዓመት በርካቶች ይሰበራል ብለው ከሚጠብቁት የዓለም ክብረወሰን መካከል የሴቶች አምስት ሺ ሜትር ቀዳሚ መሆኑ ጥርጥር የለውም። የዓመቱ ምርጥ አትሌት የሆነችው አልማዝ አያና ይህን ክብረወሰን ለማሻሻል ተስፋ የተጣለባት አትሌት ናት። አልማዝ ከ2015 የውድድር ዓመት ጀምሮ ይህን ክብረወሰን ለመስበር ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጋ አልተሳካላትም። ዘንድሮ ግን የዚህ ክብረወሰን በር እንደሚከፈትላት እያሳየች የመጣችው ድንቅ አቋም ማረጋገጫ ነው።

የቀድሞዋ የሦስት ሺ ሜትር መሰናክል አትሌት አልማዝ አያና 2015 ላይ በሻንጋይ ዳይመንድ ሊግ ስታሸንፍ በርቀቱ ያስመዘገበችው 14:14:32 ሰዓት በታሪክ ሦስተኛው ፈጣን ሰዓት ነበር። አልማዝ በጥሩነሽ ዲባባ የተያዘውን14:11:15 ሰዓት እንደምታሻሽል በርካቶች እምነት ያሳደሩባት ከዚህ ወቅት ጀምሮ ነው። አልማዝም ይህን ክብረወሰን የግሏ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት በተደጋጋሚ አሳይታለች። በወቅቱ የፓሪስ ዳይመንድ ሊግም ከክብረወሰኑ ባለቤት ጥሩነሽ ዲባባ ታናሽ እህት ገንዘቤ ዲባባ ጋር ቀጠሮ ይዘው በተነጋገሩት መሰረት መሮጥ ባለመቻላቸው ክብረወሰኑ ሳይሰበር ቀርቷል።

አልማዝ ከዚህ በኋላ ክብረወሰኑን ለመስበር ለብቻዋ ጥረት ማድረግ ጀመረች። በቤጂንግ የዓለም ቻምፒዮናም ጥረቷ ባይሳካም 14:26:83 የሆነ የቻምፒዮናው ክብረወሰን በማስመዝገብ አሸነፈች። በካቻምናው የውድድር ዓመትም ይህ ጥረቷ ቀጥሎ ሮም ዳይመንድ ሊግ ላይ 14:12:59 የሆነ በርቀቱ ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤት መሆን ቻለች። ይህም ከጥሩነሽ ክብረወሰን ከሁለት ሰከንድ ያነሰ ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህ ውድድር አልማዝ ምናልባትም ጥሩ አሯሯጭ አጋጥሟት ቢሆን ኖሮ ክብረወሰኑ ያኔ የግሏ ይሆን ነበር። በቀጣይ አልማዝ ሪዮ ኦሊምፒክ ላይ ይህን እንደምታሳካ ተስፋ ተጥሎባት የነበረ ቢሆንም ያልታሰበውንና ከባዱን የአስር ሺ ሜትር ክብረወሰን 29:17:45 በሆነ ሰዓት የግሏ አድርጋለች።

በዚያ ዓለምን ጉድ ባሰኘ ውድድር አልማዝ ከሃያ ሦስት ዓመታት በፊት ቻይናዊቷ ጁንዢአ ዋንግ ተይዞ የቆየውን 29:31:78 ክብረወሰን በሰፊ ሰዓት ልዩነት መስበሯ በአምስት ሺ ሜትርም እንድትጠበቅ አድርጓት ነበር። ሆኖም በቴክኒክ ስህተት አቅሙ እያላት ሳታሳካው ቀርቷል። አልማዝ ሪዮ ላይ በአምስት ሺ ሜትር የሰራችውን የቴክኒክ ስህተት ባለፈው የለንደን ቻምፒዮና ትደግማለች ብሎ የጠበቀ አልነበረም። ሪዮ ላይ የአስር ሺ ሜትር የዓለምና የኦሊምፒክ ክብረወሰኑን ስታሻሽል አምስት ሺ ሜትሩን ያገባደደችበት ሰዓት በተደጋጋሚ ሞክራ ያልተሳካላት የአምስት ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ለንደን ላይ አልተሳካም። አልማዝ ያለፈውን የውድድር ዓመት በጉዳት ከውድድር ርቃ ማሳለፏን ተከትሎ ክብረወሰኑ ባይሳካላትም ለንደን ላይ የብር ሜዳሊያ በርቀቱ ስታጠልቅ ያሳየችው ድንቅ አቋም በጥሩ ጤንነት ላይ ከተገኘች ዘንድሮ ልታሳካው እንደምትችል ተስፋ ተጥሎባታል።

ጆናታን ኤድዋርድስ ጎትቦርግ ላይ 18ነጥብ29 ሜትር በመዝለል ያስመዘገበው የዓለም የስሉስ ዝላይ ክብረወሰን ለሃያ አንድ ዓመታት ሳይሰበር መቆየቱ ለብዙዎች ምስጢር ነው። ይህ ክብረወሰን በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ይሰበራል ተብሎ ቢጠበቅም አልሆነም። የውድድሩ ኮከቦች አሜሪካዊው ክርስቲያን ቴይለርና ኩባዊው ፓብሎ ፒቻርዶ ድንቅ ፉክክር በዶሃ ዳይመንድ ሊግ ውድድር ይህ ክብረወሰን መሻሻል እንደሚችል ያረጋገጠ ነበር። ነገር ግን ሁለቱ ኮከቦች ከአሥራ ስምንት ሜትር በላይ መዝለል ቢችሉም ክብረወሰኑ ላይ መድረስ አልተቻላቸውም።

ፒቻርዶ 18 ነጥብ06 ሜትር በመዝለል የራሱን ክብረወሰን ከማሻሻሉ ባሻገር የአገሩን ክብረወሰን በጨበጠበት ማግስት ቴይለር 18ነጥብ04 ሜትር በመዝለል ተከትሎታል። ብዙም ሳይቆይ ቴይለር ሉዛን ዳይመንድ ሊግ ላይ አሸናፊ ያደረገውን 18ነጥብ06 ሜትር ዘሏል። ቴይለር የ2015 የውድድር ዓመትን በቤጂንግ የዓለም ቻምፒዮና 18ነጥብ21 ሜትር በመዝለል በውድድሩ ታሪክ ሁለተኛውን ክብረወሰን አስመዝግቦ በስኬት ቢያጠናቅቅም የኤድዋርድስን ክብረወሰን የግሉ ማድረግ አልቻለም።

የሚገርመው ቴይለር የ2016 የውድድር ዓመት ላይ አስራ ስምንት ሜትር መዝለል አለመቻሉ ነው። በውድድሩ ታሪክ በተከታታይ ኦሊምፒኮች ሁለት ጊዜ ማሸነፍ የቻለውና በሁለቱም እግሮቹ በመነሳት ችሎታ የሚታወቀው ቴይለር ሪዮ ኦሊምፒክ ላይ ሲያሸንፍ መዝለል የቻለው 17ነጥብ86 ሜትር ነበር። ለዚህም ተቀናቃኙ ፒቻርዶ በ2016 በጉዳት ከውድድር በመራቁ ምክንያት ነው። ፒቻርዶ ቴይለር የበለጠ እንዲሰራ የሚገፋው ተፎካካሪ እንደመሆኑ መጠን ዘንድሮ ከጉዳት ሲመለስ የሚኖራቸው ድንቅ ፉክክር ጥቂት የቀረውን ክብረወሰን እንዲሻሻል ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል።

በርካታ የአትሌቲክስ ቤተሰቦች ፖላንዳዊቷ ድንቅ መዶሻ ወርዋሪ አኒታ ቮዳርዛይክን ሲያሞካሹ በህይወት ውስጥ ሦስት ነገሮች አይቀሩም ይላሉ። እነዚህም ሞት፤ ታክስና የአኒታ ክብረወሰን ማሻሻል ናቸው። ሌሎቹን ለጊዜው እንተዋቸውና የዚህችን ድንቅ አትሌት ክብረወሰን የማሻሻል አቅም እንመልከት። አኒታ በመዶሻ ውርወራ የበላይነትን መያዝ ከጀመረች አንስቶ ስድስት የዓለም ክብረወሰኖችን ደጋግማ አንክታለች። በዚህም ልክ እንደ ወር ደመወዝ ወቅቱ ሲደርስ እርግጠኛ ሆኖ መውሰድ እንደሚቻለው ሁሉ አኒታ ውድድር ላይ ክብረወሰን እንደምታሻሽል በርካቶችን አሳምናለች።

በአስገራሚ ሁኔታ አኒታ በ2016 የውድድር ዓመት ከአንድ እስከ አስር በደረጃ ከተቀመጡ ምርጥ ውርወራዎች አስሩም የእሷ ናቸው። አኒታ ሪዮ ኦሊምፒክ ላይ በክብረወሰን ታጅባ በወርቅ ከደመቀች አሥራ ሦስት ቀን በኋላ በአገሯ ዋርሶ ከተማ ላይ 82ነጥብ98 ሜትር በመወርወር የራሷን ክብረወሰን አሻሽላለች። በ2016 የውድድር ዓመት ያሳየችው አስደናቂ ወጥ አቋምም የዓመቱ ምርጥ አትሌቶች ሽልማት የመጨረሻ ሦስት ዕጩዎች ውስጥ አካቷታል። ክብረወሰኖችን ደጋግማ በመስበሯም ውድድሩ አስደናቂና ትኩረት እንዲያገኝ አስችላዋለች። በታሪክ ሰማንያና ከዚያ በላይ ሜትር መዶሻ በመወርወር የመጀመሪያዋ ሴት የሆነችው አኒታ በዓለም ከአንድ እስከ አስር ተብለው ከተቀመጡ ክብረወሰኖች ዘጠኙን መያዟ በዚህ ዓመት ከ83 ሜትር በላይ እንደምትወረውር ተስፋ አሰጥቷታል።

2016 የውድድር ዓመት ኬንድራ ሀሪሰን ያደረገችውን በርካታ ውድድር የተመለከተ በያዝነው የውድድር ዓመት የራሷን ክብረወሰን አትሰብርም ብሎ ለመገመት ይከብደዋል። ድንቅ ፍጥነት፤ ግሩም ቴክኒክ መለያዋ የሆነው ሀሪሰን የወቅቱ የርቀቱ ኮከብ አሜሪካዊት ለመሆኗ በርካታ ማሳያዎች አሉ። ሀሪሰን ባለፈው ዩጂን ዳይመንድ ሊግ ላይ ስታሸንፍ 12ነጥብ24 በማስመዝገብ የአሜሪካን ክብረወሰን አሻሽላለች። በዚህ ውድድር ያሳየችው ድንቅ አቋምም በርካቶች ለሃያ ስምንት ዓመታት በዮርዳንካ ዶንኮቫ ተይዞ የነበረውን 12ነጥብ21ክብረወሰን እንደም ትሰብር ተስፋ አድርገው ነበር። ሀሪሰን አሜሪካን በሪዮ ኦሊምፒክ ለመወከል በተደረገው ውድድር ስድስተኛ ወጥታ ባይሳካላትም በለንደን የበጎ አድራጎት ቻምፒዮና የዓለም ክብረወሰን የሆነውን ሰዓት በአንድ ማይክሮ ሰከንድ አሻሽላዋለች። በ2016 ምርጥ አስር ሰዓቶች መካከል ስምንቱን የያዘችው ሀሪሰን በዚህ የውድድር ዓመት መቶ ሜትርን 12ነጥብ15ና ከዚያ በታች ልትሮጠው እንደምትችል ተስፋ ተጥሎባታል። አሁን የያዘችውን ክብረወሰን ለንደን ስታድየም ላይ ማስመዝገቧ ይታወሳል። በዚህ ዓመት ክረምት ላይ በዚሁ ስታድየም በዓለም ቻምፒዮና ክብረወሰኑን ለማሻሻል ብትጠበቅም አልተሳካላትም።

በሪዮ ኦሊምፒክ አዲስ ክስተት ከሆኑ አትሌቶች መካከል ደቡብ አፍሪካዊው ዋይድ ቫን ኒከርክ አንዱ ነው። ይህ ወጣት አትሌት በሪዮ ኦሊምፒክ በሴት ሃያቱ እየሰለጠነ የአራት መቶ ሜትር የዓለም ክብረወሰን በማሻሻል ወርቅ ማጥለቁ ይታወሳል። ኒከርክ በሪዮ ኦሊምፒክ ይህን ትልቅ ታሪክ ሲሰራ በውድድሩ ታላቅ የሚባሉትን ኪራኒ ጄምስና ላሻውን ሜሪትን ከስምንተኛው መም በመነሳት መሆኑ ክብረወሰኑን ለአስራ ሰባት ዓመታት ይዞ የቆየውን ማይክል ጆንሰን ሳይቀር አስደንቋል። ኒከርክ 43ነጥብ03 የሆነውን ክብረወሰን በዚህ ዓመት የማሻሻል አቅም እንዳለው የሪዮ ኦሊምፒክ አስደናቂ ብቃቱ ብቻ ማረጋገጫ ይሆናል።

 

ቦጋለ አበበ

Published in ስፖርት

 

መስቀል በዓዲግራት                                                  መስቀል በኢሮብ

 

የጉዞ ማስታወሻ

ጉዟችንን ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ትግራይ ክልል አድርገናል። መቐለ እንደደረስንም በየዓመቱ ለየት ባለና በደመቀ ሁኔታ መስቀል ወደሚከበርባት ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 880ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከመቐለ 120 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ዓዲግራት ከተማ አቀናን። ዓዲግራት የትግራይ ምሥራቃዊ ዞን ስትሆን ስያሜዋም «ዓዲ» ማለት ቦታ ሲሆን «ግራት» ደግሞ ሰፊ የእርሻ ቦታ ማለት ነው። ዙሪያዋን የከበቧት አይጋ፣ አሲምባ፣ የምጉላት፣ ኣሎቃ እንዲሁም ገረኣልታ ሰንሰለታማ ተራሮች የከተማዋን ውበት አጉልተው ያሳያሉ። ማራኪ ገፅታን ካላበሷት ተራሮች በተጨማሪ ከአለት የተሰሩ ገዳማትም ይገኙባታል።

ከተማዋ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተቆረቆረች ሲሆን የመስቀል በዓልም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንደሚከበር ይታመናል። በደማቅ ሁኔታ ሲከበር ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ ነው። የመስቀል በዓል ለማክበር በዓዲግራት100 ኪሎሜትር ዙሪያ የሚገኙ አካባቢዎች ዕለቱን የሚያውሳ የባህል ጭፈራና ሙዚቃቸውን እየሞዘቁ ሲተሙ ተመለከትን። ኩናማ፣ ኢሮብ፣ አክሱም እና ሌሎቹም በዓሉ በሚከበርበት የዓዲግራት ገጠራማ አካባቢ በሆነው ድብላ ስዔት ቀጠር ቀበሌ እየዘለቁ ነው።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለግብርና ስራ የሚጠቀሙበትን መሳሪያዎች ይዘዋል። ማጨብ ጨቢያ፣ ሸፋ ፣ ሸፋ ሸፎና ሌሎችንም ለበዓሉ ማድመቂያነት ተጠቅመዋል። ሁሉም የአካባቢው መለያ አለባበስም የለበሱ ሲሆን ፀጉራቸውም በተመሳሳይ ተሾርበዋል። ቀልቤን ወደሳበኝ አንድ ጭፈራ እግሮቼ አመሩ። ወጣቶቹ የመጡት ከክልተ አውላሎና አፅቢ ሲሆን ጭፈራቸው የሬጌ ስልትን የተከተለ በመሆኑ በአካባቢው መጠሪያ ይኖረው እንደሁ ለማወቅ አንድ ወጣት ጠጋ ብዬ ጠየኩት እሱም «ሁራ ሰለስተ» እንደሚባል ገለፀልኝ የእግር አረጋገጣቸው አንድ ጊዜ ሁለት፣ ቀጥሎ አንድ፣ ከዚያም ሦስት ጊዜ እያነሱ የሚረግጡበት የጭፈራ ስልት ነው። አሁን ወደ ቦታው የሚመጡ አካባቢዎች መጠን እየጨመረ ጨዋታውም እየደራ ነው ።

ከጭፈራው ጠጋ ሲሉም ሜዳው ላይ ከየአካባቢው የመጡትን ከብቶች እረኞቹ ትግል እንዲገጥሙ ሲያደርጉ ተመለከትን። በትግሉ ያሸነፈው ከብት እረኛ በደስታ ብርሃን ፊቱ ሲበራ ተሸናፊው ለከርሞ ለማሸነፍ ሲዝት ይታያል። ክዋኔው ብቻ ምን ልበላችሁ እያንዳንዱ ነገር መንፈስን የሚሰርቅ አንዳች ኃይል አለው። ቅኝቴን አላቆምኩም ዓይኖቼ ማማተራቸውን ቀጥለዋል። በሌላ ወገን ደግሞ በፈረስ ውድድር እሽቅድድም የገቡ ወጣቶችን አየሁ። ወጣቶቹ ከተቻለ አሸንፎ የአካባቢዋን ቆንጆ ኮረዳ ለማማለል እሱ ካልሆነም ዓመቱን ሙሉ «እርሱ እኮ አንደኛ ነው። የዓመቱ ጀግና ነበር» በሚል ሴቶች ልብ ውስጥ መግባቱ ታላቅ ሽልማት መሆኑን ሰማን። በመሆኑም በዚህ ስሜት ውስጥ ሆነው ይህንን ስም ለማግኘትና ይዞ መቆየት ቀላል አይደለምና በማሸነፍ ወኔ በተዋቡ ፈረሶች ላይ ተቀምጠው ይጋልባሉ። ለጊዜው ምልከታዬን ገታ በማድረግ እንደው ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች የሚካሄዱ ሥርዓቶች ካሉ በሚል ትዕይንቶቹን ለመታደም የመጡ የአካባቢውን ነዋሪዎች አነጋገርኩ።

የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ የዕድሜ ባለፀጎች እንደነገሩን በዕለቱ ወንዶችም ሆኑ ሴቶችም ቅቤ የሚቀቡበት ይህ ብቻ አይደለም። ሀብትን ያበረክታል ተብሎ ስለሚታሰብ ከብቶችም ቀንዳቸው፣ ጫንቃቸው እንዲሁም ጭራቸውን ቅቤ የሚቀባበት ዕለት ነው። በበዓሉ ያለውም ሆነ የሌለው በአንድነት ሰብሰብ ብሎ አርዶ በጋራ እንደሚቋደስም ነገሩኝ። ታዲያ አንዲት እናት እንዳሉን በተዘጋጀው ማዕድ ዙሪያ ከዘጠኝ ያልበለጠና ያላነሰ ሰው ነው የሚሰበሰበው።

ለእነርሱም ተወዳጅ የሆነውን የባህል ምግብ «ግዕዝሚ» እና «ጥህሎ» ይቀርባል። ግዕዝሚ ማለት ፈረንጆቹ ሀት ዶግ እንደሚሉት ዓይነት ነው። ሰውም የቀረበለትን ምግብ በምኒልክ ኩባያ በቀረበው ጠላ (ስዋ) እና ጠጅ (ሜስ) እያወራረደ የሆድ የሆዱን ያወጋል። ይህ ብቻም አይደለም ስለሀገራዊ ጉዳዮች ይመክራሉ፤ የተጣላ ካለም ያስታርቃሉ። በአካባቢው በብዛት ወንዶች የመታየቻው ምክንያት ምን ይሆን? ብዬ ጥያቄ ያቀረብኩለት ወጣት እንደመለሰልኝ፤ በዓሉ አብዛኛውን ጊዜ ከከብቶች ከመጠበቅና በዛው ለችቦ የሚሆን እንጨት ከመልቀም ጋር የተያያዘ ነው። ይህም በጨዋታው በስፋት የሚታዩት ወንዶች እንዲሆኑ አድርጎታል። በዚህም ወጣቶች ሲጫወቱ አባቶች ደግሞ ራቅ ወዳለ ጥላ አካባቢ በመሄድ ይወያያሉ። የዓዲግራት ምልከታዬን እዚህ ላይ ቆም አድርጌ በዓሉ በድምቀት ወደሚከበርባት ኢሮብ ልውሰዳችሁ።

ኢሮብ እንደደረስን ያወቅነው በርቀት ለበዓሉ የሚሆን «ግዕዝሚ» የሚጠበስበት «ሶላ» የተባለ ሥርዓት ሲካሄድ በሚወጣው ጭስ ነው። ቦታው ላይ እንደደረስን በደስታ የተቀበሉን ነዋሪዎች «መስቃሊቴና» በምትባል ቦታ ላይ ለከብቶች ክብር ተብሎ የተሰዉ ፍየሎችን አርደው እየተዘገጃጁ ነበር። በኢሮብ ከዘመን መለወጫም በላይ የሚከበረው የመስቀል በዓል ሲሆን የከብቶች የክብር በዓል እንደሆነ ነገሩን። የኢሮብ ወረዳ ዳህዋን ከተማ ነዋሪዎች እንደነገሩን በዚህ በዓል ከብቶች ክብር የሚያገኙበት ነው። ከዘመን መለወጫ እስከ መስቀል ባለው ጊዜ ከብቶች በአካባቢው ልዩ ክብር ይሰጣቸዋል አይታረዱም። ይልቁንም ከታረደው ፍየል ደም ግራና ቀኝ በኩል ባለ ጆሮ ግንዳቸው ላይ ይቀባሉ። በተመሳሳይ ቅቤም ቀንዳቸው፣ ጫንቃቸውና ጭራቸውን ይቀባሉ።

በዚህ ዕለት በአንድ ቦታ የተሰበሰቡት ከብቶች እየታለቡ ግዕዝሚ በመስራት የተጠመዱት ወንዶች ይጠጣሉ። ሴቶች በማጀት ገንፎ ያገነፋሉ። ልክ ከረፋዱ አራት ሰዓት አካባቢም የአካባቢው ወጣቶች በአካባቢው ባለ ቤተክርስቲያን ዙሪያ ዕለቱን መሠረት ያደረገ ዘፈን በመዝፈን ይዞራሉ ሽግ በመያዝም ይሞዝቃሉ።

ከመካከል ድምፁ መረዋ የሆነው የተመረጠ ወጣት «ሆ ሆ ሆያዬ» ሲል ሌሎች «ሆ ሆ ሆዬ» በሚል ይቀበሉታል። በሦስተኛው ዙራቸው እንደ ውድድር ይሽቀዳደማሉ። እንዲህ እንዲህ እያሉ እስከ ቀኑ 10 ሰዓት ድረስ በከበሮ በታጀበ ሃይማኖታዊ መዝሙርና ጨዋታ ያሳልፉታል። በሌላ በኩል ታዲያ ግዕዝሚ ሲሰሩ ሲመገቡ የዋሉት ወንዶች በተራቸው ወደ ገንፎ ሲሄዱ ሴቶችም ወደ ግዕዝሚ ያመራሉ። ዓመቱን የልምላሜና የሀብት እንዲያደርገውም ወንዶችም ሴቶችም ቅቤያቸውን አናታቸው ላይ ያሳርፋሉ። በኋላም ሁሉም በየቤቱም ችቦ በማውጣት «አኩኬ አኩኬ» ይላል። ይህንኑ አብሮ ተከባብሮ የመኖር ባህላችንን ያዝልቅልን በማለት የዓመት ሰው እንዲለን እየተመኘሁ በቀጣይ ስለ ሌሎች ባህላዊ ክዋኔዎች ላስቃኛችሁ ቃል ገባሁ።

 

ፍዮሪ ተወልደ

Published in መዝናኛ

የሶሻል ኮሚቴ ምርጫ በተካሄደበት ወቅት፤

 

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች እና አመራሮች ሰሞኑን ለአራት ቀናት ውይይት አድርገዋል፡፡ በወቅቱም ተቋሙ በአሁኑ ወቅት እያከናወናቸው የሚገኙትን እና ስለ ቀጣይ እቅዱ፤ እንዲሁም ለፈጣን ለውጥ ስለሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶች እና ተቋማዊ ለውጥ በፍጥነት ማስኬድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡ በቡድን ተከፋፍለው ባካሄዱት ውይይትም ከ60 በላይ አንኳር ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

ለአብነትም አዳዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል መሠረተ ልማት እና ለተማሪዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እስከምን ድረስ ተሟልቷል?፤ የምርምር ሥራዎችን ወደ ገበያ ማውጣት እና በቢዝነስም ተጠቃሚ መሆን ላይ የተሰጠው ትኩረት ምን ይመስላል?፤ የማስተማሪያ መጽሐፍት ግዥ ከተማሪዎች ቅበላ ጋር ማጣጣም እስከምን ተሰርቷል?፤ የቤተ ሙከራ ዕቃ ግዥ ሁኔታስ ምን ይመስላል?፤ ማበረታቻ እና ጥቅማጥቅም በሚገባ መልኩ አልተዘረጋም፤ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ስለምን በዲፕሎማ ያሰለጥናል? ስለምን በዲግሪ እና ከዚያ በላይ አያሰለጥንም፤ መሠረተ ልማት ሲከናወን አካል ጉዳተኞችን ከማገናዘብ አኳያ ምን ታስቧል? ህግን ያልተከተለ እና ፎርጅድ ግብዓቶች ግዥ ተፈጽሟል፡፡ ይህ መፈተሽ አለበት ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም ጥብቅ ግምገማ እና ክትትል ሥርዓት መዘርጋት፣ ለባለሙያዎች ተከታታይ ስልጠናዎች መስጠት፣ ማህበራዊ ሕይወትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ «ሶሻል ኮሚቴ» አለመኖር፤ ትምህርታዊ ጉዞ በአዲስ አበባ ብቻ መገደቡ እና ቀጣይ እቅድ ምን ይመስላል? ሺሻ እና ጫት ቤቶችን የመሳሰሉ በዩኒቨርሲቲው አቅራቢያ ስለሚገኙ እነዚህን ለማስወገድ ከሚመለከታቸው አካላት ቅንጅታዊ አሠራር ለመዘርጋት ምን ታስቧል?፤ ከቅጥር እና ዝውውር ጋር የሚፈጠሩ አሻጥሮችን እንዴት ማቃለል ይቻላል? ዩኒቨርሲቲው ለምን የራሱ የምንዛሬ ቢሮ አይኖረውም? የዩኒቨርሲቲው አጥር በመፍረሱ ተቋሙን ለአደጋ የሚጋልጥ ችግር ስለሚኖር ምን ታስቧል? ለተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታ እጥረት መኖር፤ የማበረታቻ ሥርዓት እና አሠራር ተቋሙ ባለመዘርጋቱ ሠራተኛው ላይ ተነሳሽነት እንዳይፈጠር አድርጓል። ሲሉ በአራቱ ቀናት ውይይት ያነሷቸው ጥያቄዎች ነበሩ፡፡

ዶክተር ደመወዝ አድማሱ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፤ ትምህርታዊ ጉብኝቶች ቀደም ብለው የታቀዱ እና ከሥርዓተ ትምህርት ጋር የተጣጣሙ መሆን አለባቸው ይላሉ፡፡ ችግሩ ግን መጨረሻ ላይ ተደራርበው ስለሚመጡ በአንድ ጊዜ ማስተናገድ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ሆኖም በተጨናነቀም ሁኔታ ቢሆንም ለማስተናገድ ጥረት ሲደረግ መቆየቱንም ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ በዘለለ የልምድ ልውውጥ የትምህርት አንዱ አካል እስከሆነ ድረስም አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ጉብኝት እንደሚደረግ ይገልጻሉ፡፡ በ2010 ሁሉም የትምህርት ክፍል በእቅዳቸው መሠረት እንደሚስተናገዱ ነው ያስገነዘቡት፡፡

ለትምህርት ጥራት ሲባል የልምድ ልውውጥ ለማድረግ በአዲስ አበባ ብቻ መወሰኑ ጉዳት ወይስ ጥቅም ለሚለው ጥያቄ ግን በሰከነ መንፈስ ማየት እንደሚገባ ይጠይቃሉ፡፡ በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ ያሉ አማራጮችን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ማማተር የተገደበ እንዳልሆነ ነው የሚናገሩት፡፡ ፋይዳቸው የጎላ እና በትምህርት ውጤታማነት ላይ የሚጨምረው አንዳች ፋይዳ ካለም ዩኒቨርሲቲው አቅሙን አሟጦ እንደሚጠቀም አስገንዝበዋል፡፡

ዶክተር ኤላዛር ታደሰ በዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ በምርምር ዘርፉ ጥራቱንና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ምርምር ማካሄድ ለድርድር መቅረብ የሌለበትና ለዚህም ሲባል አስፈላጊ ክትትል፣ ግምገማ እና ቅኝቶች እንደሚደረግ ይገልፃሉ፡፡

የምርምር ሥራዎች ማበረታቻ መመሪያ የለውም በማለት መምህራኑ ለሚጠይቁት ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። በዋናነት አንድ መምህር ጥናትና ምርምር ማካሄድ እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት ሙያዊ ግዴታ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ማበረታቻ ማለት ደግሞ በብር ብቻ የሚተመን መሆን የለበትም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ይህ ለኅብረተሰቡ የሚበረከት ሙያዊ ግዴታ በመሆኑ ብር መቅደም የለበትም፡፡

ጥናትና ምርምሮች ሙያዊ የሆነ ግዴታ በመወጣት ከኅብረተሰቡ እና ከባለሙያዎች ምስጋና እና እውቅና ለመቸር በር ይከፍታል፡፡ ይህ ከምንም የላቀ ማበረታቻ ነው፡፡ ምናልባትም ገንዘብ በመጨረሻው ማበረታቻ ሊሆን እንደሚችል ነው የሚናገሩት፡፡ ወደ ከተማዋ መውጣት ሳያስፈልግም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ቀድሞ የራስን ችግሮች ማቃለል እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ በመቀጠል ደግሞ የከተማዋን ሕዝብ ብሎም አገሪቱን ከተሞች ማዕከል ያደረገ ሰፋፊ ጥናቶች ማድረጉ የማይገደብ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ በሂደትም ምርምር የሚያከናወኑ ሰዎች ተጠቃሚታቸውን ማረጋገጥ እንደሚቻልም ዶክተር ኤላዛር ያስረዳሉ፡፡

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና እንደሚሉት፤ ዩኒቨርሲቲው በየጊዜው ከከተማዋ እና አገሪቱ ከጣለችበት ተልዕኮ አኳያ የተሻሉ አሠራሮችን መቀየስ፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን መቀመር፣ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ምርምሮችን ማከናወንና ለተጠቃሚው ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም ከጊዜው ጋር የሚጣጣም አሠራር መቀየስና መተግበር እንደሚጠበቅበትና ለዚህም እየተጋ መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፤ ጥራቱን ያልጠበቀ እና ያለአግባብ ግዥ የሚፈፀም ከሆነ በማናቸውም መስፈርት ተጠያቂነት እንደሚኖር እና መልካም አስተዳደር ማስፈን እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡ የመንግሥት ንብረት በማናቸውም ሁኔታ መባከን እንዳይኖር ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ በቀጣይ ግን አፈፃፀማቸው እየታየ ያልተማከለ አሠራር እንደሚኖር አስገንዝበዋል፡፡ ችግሮች እና አስቸጋሪ ካልሆነ በስተቀር ከማዕቀፍ ግዥ ውጪ በሆነ መልኩ ፕሮፎርማ መሰብሰብ እና ሕግን ያልተከተለ ግዥ እንደሚቆም ነው የሚያስገነዝቡት፡፡

የጂም ክፍሎችን ለመሰብሰቢያ መጠቀሙ አስፈላጊ ሆኖ ሳይሆን ተቋሙ ካለበት ወቅታዊ ችግር ነው፡፡ በቀጣይ ግን በቅርቡ 800 ተሰብሳቢዎችን የሚይዝ አዳራሽ በግንባታ ላይ መሆኑን በመጠቆም ሠራተኞቹ ጂሙ ለመሰብሰቢያ መጠቀሙ አግባብ እንዳይደለ ባቀረቡት ሃሳብ ይስማማሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ በአንድ ማዕከል ብቻ ስለሆነ ዩኒቨርሲቲው የራሱ ሆነ የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ሊኖር አይችልም፡፡ በአሁኑ ወቅት ከከንቲባው በስተቀር በማናቸውም ቢሮ መሰል አሠራር እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና የከተማ አስተዳደሩ ለዩኒቨርሲቲው ቅድሚያ የሚሰጥ በመሆኑ የጎላ ችግር እንደማይኖር ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት፤ የማበረታቻ ሥርዓት እና አሠራር ተቋሙ አለመዘርጋቱ በሥራው ላይ ጫና እንደሚፈጥር በመጠቆም ጠንካራ ሠራተኞችን የሚበረታቱ አሠራር ተግባራዊ እንደሚደረግም ይጠቁማሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲው የሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችን ሥርዓተ ትምህርት የሚከተል አይደለም። ነገር ግን የከተማዋን ችግር በዋናነት የሚያቃልሉ የትምህርት ክፍሎች እንደሚከፈትም ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህም የሚመጥኑ ሥነምግባር፣ ክህሎት እና በእውቀቱ የተመሰገኑ መምህራን እንደሚቀጠሩ እና ያለአግባብ በውስልትና የሚቀጠሩ ካሉ ተጠያቂነት እንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡

2010 .ም አዳዲስ ዲፓርትመንቶች እንደሚከፈቱና በ2011 .ም ደግሞ በሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ማሰልጠን እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡ የተማሪዎችን የቅበላ አቅም ማሳደግ፤ መሠረተ ልማትን ማሟላት እና ተወዳዳሪነት የሚያመጣ እንደሆነ ነው የሚያስገነዘቡት፡፡ ዲፕሎማ መርሐግብር ማሰልጠኑም ክፋት የሌለው እና ቀድሞውን ዩኒቨርሲቲው ይዞት የመጣ ተግባር ስለሆነ ይህ ለመከራከሪያ መቅረብ እንደሌለበት ይናራሉ፡፡ የሶሻል ኮሚቴም በውይይቱ ማጠናቀቂያ ላይ መቋቋሙን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዶክተር ብርሃነመስቀል ገለፃ፤ ዩኒቨርሲቲው ከጀመረው የለውጥ ጉዞ አኳያ የከተማዋ መስተዳድር ሊደግፈን ይገባል፡፡ ከክፍለከተማ ጀምሮ ያሉ የሥራ ኃላፊዎች ለከተማዋ ብቸኛ የሆነውን ዩኒቨርሲቲ ትኩረት እንዳይነፍጉ አሳስበዋል፡፡ የማስፋፊያ ቦታ እና ተጨማሪ ካምፓሶችን በመስጠት፣ የግብዓት አቅርቦት እጥረትን ለማቃለል ትኩረት በማድረግ፣ ተገቢ በጀት መመደብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ሠራተኛው ተቋሙ የተሻለ ሆኖ ለማየት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ በውይይቱ አያሌ ነጥቦች የተነሱ በመሆናቸው ለቀጣይ ተግባራት የሚገነቡ እና የተቋሙን ሁለንተናዊ ለውጥ የሚያፋጥኑ በመሆናቸው ትኩረት እንደሚደረግም አረጋግጠዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይስሐቅ ግርማይ በበኩላቸው፤ የከተማ አስተዳደሩ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ለከተማ አስተዳደሩም ሆነ ለአገሪቱ የሚኖረው ፋይዳና ትርጉም ዘርፈ ብዙ በመሆኑ ከመቼውም በበለጠ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሠራተኛው ተነሳሽነት እና ውይይቱም ተቋሙ ወደ ለውጥ ጉዞ በፍጥነት የሚገባበትን መንገድ እየተከተለ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ለዩኒቨርሲቲው አስፈላጊ ድጋፍ በማድረግም ተቋሙ ዓለም አቀፋዊ ብርቱ ተፎካካሪ እንዲሆን ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡

 

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

Published in ማህበራዊ

 የቀድሞ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ

 

              

   የክብር አምባሳደር          ወይዘሪት ሕይወት አዳነ         ወጣት ብሩክ ሚፍታህ            ወይዘሪት መሠረት ብርሃኑ

 

  

ሼህ መሀመድ ሸሪፍ ሀሰን                  ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

በአንድ ሀገር ውስጥ ልማት ለማምጣት ሰላም ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ቁጥር አንድ ተግባር ነው፡፡ በዚህም ስለ ሰላም ማሰብ በራሱ ውስጣዊ መረጋጋትን የሚፈጥር ኃይል እንዳለው ብዙዎች ሲናገሩ ይሰማል፡፡ ይህ አስተሳሰብ የፍጡራን ሕይወትን በተሻለ ሁኔታ ለመምራት በሚያስችል ውሳኔ ላይ ይመረኮዛል፡፡ ማለትም በሰላም የመኖርና ያለመኖር ምርጫ በግለሰቦች እጅ ላይ ይሆናል፡፡

የግለሰቦች ሰላም መሆን ድምር ውጤት በሀገር ሰላም ላይ የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ እንደሚሆን ይታምናል፡፡ ከግለሰቦች አልፎ በሀገር እያንዳንዱ እንቅስቃሴና የመኖር ህልውናን የሚያረጋግጠውን ሰላም ለማስጠበቅ ከድሮ ጀምሮ የነበረውን ታሪክ ከመዘከር ባለፈ የትናንቱን ለነገ በተሻለ ሁኔታ ለማስቀጠል ዛሬ ላይ መስራት ይገባል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም የቀድሞ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ የሚሰሩት ሥራ ተጠቃሽ ነው፡፡ እኛም ከሰሞኑ የሰላም አዳራሽ በሚል ባስገነቡት አዳራሽ ውስጥ የዓለም የሰላም ቀንን አስመልክቶ በነበረው መርሀ ግብር ላይ በመገኘት ያገኘነውን ልናካፍላችሁ ወደድን፡፡

ወቅታዊ ሁኔታ

የክብር አምባሳደር አቶ ምዑዝ ገብረሕይወት በተለያዩ ሕዝባዊ አደረጃጀቶች ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ በዚህም በሀገሪቱ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ ናቸው። በዚህም ሰላም በኢትዮጵያ ቀድሞና ዘንድሮን እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ያሉ ችግሮችን ሲናገሩ፤ በሀገሪቱ ብዝሀነት እንዳለ በመታመኑ ብዝህነቱ ተከብሮና ተጠብቆ ለብዙ ዓመታት ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ ግን በርካታ ለውጦችና የሚታዩ ዕድገቶችን ማስመዝገብ ቢቻልም ይህንን በሚፃረር መልኩ የሚታዩ ችግሮች እንዳሉ አይካድም ይላሉ፡፡ ችግሮቹ በአንድ በኩል የግንዛቤ ማጣት ያመጣቸው ሲሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የውጭ ኃይሎች የሀገሪቱን ሰላም መሠረት በመናድ ዕድገቷን ለመጎተት በሚያደርጉት ሩጫ የመጡ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

ከተጠቀሱት ችግሮች ውጪም በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱን ሰላም እያወከ የሚገኘው መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን መንግሥት ከወረዳ እስከ ፌደራል ድረስ ይህንን ያስፈፅማሉ ሕዝቡንም ያገለግላሉ በሚል ባስቀመጣቸው አመራሮች ነው። ምንም እንኳ እነዚህ አመራሮች በቁጥር ሰፊውን ድርሻ ቢይዙም ብዙ በጀት ተመድቦ ቢቀመጡም፤ አንዳንድ ኃላፊነት የማይሰማቸው በመኖራቸው ኅብረተሰቡ እያነሳቸው ያሉ ሰፋ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲመጡ እያደረጉ ነው፡፡ ይህንን እንዲያግዙ የተቋቋሙ ሕዝባዊ አደረጃጀቶችም የሚጠበቅባቸውን ተግባር በአግባቡ ሲወጡ አይስተዋልም። «በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎች ላይ እንዳንታገል የማኮላሸት እንቅስቃሴ የሚያርጉ በመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ቦታ ላይ የተቀመጡ አሉ፡፡» በማለት ያሉትን ችግሮች ይናገራሉ፡፡

እንደ አቶ ምዑዝ ገለፃ፤ ሕዝባዊ አደረጃጀቱ እንዲዳከምና ሞራሉ እንዲወድቅ፤ በዚህም ትግል እንዳይደረግ ፍላጎታቸው የሆኑት ኃላፊዎች ከሦስቱ ክንፎች አንዱና ዋነኛው የሆነው የሕዝብ ክንፍ በማዳከም የሕዝቡ ጥያቄዎች በተደራጀ ሁኔታ እንዳይነሱ በማድረግ ላይ ናቸው። በዚህም ችግሮች ሳይፈቱ እንዲከርሙ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ይህም ሕዝቡን የሚያነሳሳ በመሆኑ መንግሥት ይህን መሰል ተግባር ላይ የተሰማሩ አመራሮችን ሀይ ሊላቸው ይገባል፡፡ በተለይም ወደ ኃላፊነት የሚመጡ አካላትን በተገቢው መንገድ መመርመር ካልተቻለ በአሁኑ ወቅት ሹመት እየሆነ ያለው አንዱ የሌላውን ችግር መሸፈኛ ነው፡፡ ይህም በሁለት ቢላዋ እየበሉ ያሉ የሚመስሉ አመራሮች መኖርና ታርጋቸውን ቀይረው የተቀላቀሉ አካላት እንዳሉ ማሳያ መሆን ይችላል፡፡ በዚህም ሕዝብን ለአመፅና ለሁከት እየገፋፉ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡

ከብራቩራ አፍሪካ የመጣችው ወይዘሪት ሕይወት አዳነ እንደምትናገረው፤ አሁን አሁን የሚስተዋሉት ችግሮች የሰላምን ትርጉምና ምን ያክል አስፈላጊነት ካለማወቅ ከስሜታዊነት የመነጩ ናቸው፡፡ ሁሌም ቢሆን ተረጋግቶ የሚያስብ ሰው ችግሮች በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንደሚችሉ ያስባል፡፡ እዚህ ምድር ላይ ያለ ማንም ሰው ሰላም አያስፈልግም ብሎ ሊደራደር አይችልም፡፡ ነገር ግን ይህንን ባለመገንዘብ የሚደረጉ ጥፋቶች ለትውልድ የሚቀር መጥፎ ጠባሳን ጥለው ያልፋሉ፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ ሲያነሳቸው የሚደመጡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሊነሱ የሚገባው በመድረኮች እንጂ በአመፅ ሊሆን እንደማይገባ ትመክራለች።

ከአትራኮሰ ጥበብ ማህበር የመጣው ወጣት ብሩክ ሚፍታህ በበኩሉ ችግሮች የሚከሰቱት መግባባት ባለመቻል ነው፡፡ እንደ ሀገር ያለውን ነገር መመልከትና የነበረውን ታሪክና ባህልም ማሳደግ አለመቻሉ በአሁኑ ወቅት አልፎ አልፎ የሚታዩ ችግሮች አስከትሏል፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት የሚነሳውም ችግሮች ሲፈጠሩ እልባትን የሚያበጁ የተከበሩ ሰዎች ቢሆኑም ይህን ባህል ግን ጥቅም እንደሌለው ችላ በመባሉ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን ይናገራል፡፡

መጋቢ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ በአንድ ወቅት «የቀድሞ ሰዎች ስለ ሰላም ሳያወሩ በሰላም ኖሩ አሁን ስለ ሰላም እያወራን ነው ግን ሰላም አጥተናል» ብለው እንደነበር ወጣቱ ያስታውሳል፡፡ ቀጠል አድርጎም ችግሮቹ ብልጭ ድርግም የማለታቸው መንስዔ አንዳንድ ጊዜ ከወሬ የዘለለ መሬት ላይ የወረደና በተግባር የሚታይ ሥራ ባለመኖሩ መሆኑን ይገልፃል፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት በማውራት ብቻ የሚመጣ ለውጥ አይኖርም፡፡ የችግሮቹም ምንጭ አለመተዋወቅ ነው፡፡ በዚህም የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ወጣቱ ምን ይፈልጋል? በሚል ለይቶ ከመስራት ይልቅ እነርሱ የሚፈልጉትን ብቻ መጫን ተያይዘውታል ሲል አሉ የሚላቸውን ችግሮች ያመላክታል፡፡

ወጣቱን አቅርበው እያነጋገሩና የሚያስፈልገውን እየሰጡት አይደለም፡፡ በስንት አንድጊዜ የሚፈጠሩ መድረኮችም ወጣቱ ሀሳቡን እንዲያንሸራሽርና ለችግሮች በጋራ መፍትሄ የሚያመላክት ሳይሆን እንዲሰማ የሚያስገድድ ባህሪ ያላቸው መሆናቸውን ወጣት ብሩክ ይናገራል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለችግሮቹ መፍትሄ ማጣት ጋር ተመሳሳይነት ያለው አንድ ታሪክንም እንዲህ ሲል ያትታል «ሰውየው የኤሌክትሪክ ሠራተኛ ቢሆንም የማያምረው ድምፁ ሳይበግረው ዝም ብሎ ይሞዝቃል፡፡ አብረውት የሚሰሩ ባልደረቦቹም ይህን ለምደው ይቀበሉታል፡፡ እናም ከዕለታት በአንዱ ቆጥ ላይ ሆኖ ሲሰራ ኤሌክትሪክ ይይዘዋል፡፡ እናም 'ኧረ ጎበዝ ኧረ ጎበዝ' ሲል ባልደረቦቹም የተለመደው ዘፈኑ መስሏቸው 'እህ ምነው' እያሉ ይቀበሉት ጀመር፡፡ 'መሞቴ ነው' እያለ እያለ ችግር ላይ እንደሆነ በመግለፅ የእርዳታ ጥሪውን ሊያሰማ ቢሞክርም 'ለሀገርህ ነው' በሚል የእውነትም ሊሞት በሚያጣጥርበት ወቅት ቀድሞ ደጋግሞ ያሰማቸው የለመዱት አጉል ድምፁ ሳይደርሱለት እንዲቀሩ አደረጋቸው»

አላግባብ የሆነ ልማድ ትክክለኛ እርዳታ በሚያስፈልገው ወቅት እንዳያገኝ አድርጎታል፡፡ በአሁኑ ወቅትም መንግሥትና ወጣቱ መግባባት ያለመቻላቸው ምክንያት አንዳንድ በሥራ ኃላፊነት ቦታ ላይ የተቀመጡ አካላት በአግባቡ መግባባት አለመቻላቸው መሆኑን ያብራራል፡፡

ሌላዋ የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሪት መሠረት ብርሃኑ የሕዝባዊ አደረጃጀት የሆነው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ፎረምና አቤቱታና ቅሬታ የሕዝብ ክንፍ አባል ናቸው፡፡ እርሳቸው በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ስላለው ሁኔታ እንደሚናሩት ሰላም በብዙዎች ዘንድ እንደ ቀላል ቢታይም ነገር ግን ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎበት የሚመጣ ትልቅ ዋጋ ያለው የሀገር መሠረት መሆኑን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚታየውም ሰላም የቀድሞ አባቶች ሕይወታቸውን ጭምር ከፍለው ያበረከቱት ታላቅ ስጦታ በመሆኑ «በምን ዓይነት መልኩ ጠብቀን ማቆየት አለብን የሚለውን ልናስብበት ይገባል» በማለት ይናገራሉ፡፡

ሰላምን የሚሰብከው አካልስ የዕውነት የሰላም ሰባኪ ነው ወይ? የሚለውን ቆም ብሎ ማየት ሌላው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጥያቄ መሆኑን ነው ወይዘሪት መሠረት የሚናገሩት፡፡ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችም በኃላፊነት ቦታ ላይ በተቀመጡ አካላት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ለሕዝቡ በቅንነት ከማገልገል ይልቅ ማንገላታትን መሠረት አድርገው መስራት ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል፡፡ እንደ ወይዘሪት መሠረት ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት የሚታዩ ችግሮች ትክክለኛ ምንጫቸው የሥልጣን አተያይ ነው፡፡ ምንም እንኳ ፖለቲካ ብዙ ነገሩ የተወሰደው ከቅዱስ መጻሕፍቶች ቢሆንም ይህንን እውነት ግን በተግባር ማዋል ላይ በአመራሩ ክፍተት ይስተዋላል፡፡ ይህም የሚያመላክተው ችግሩ በሰፊው የሚስተዋለው በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ መሆኑን ነው፡፡ አንዳንዶቹ የተቀመጡበትንም ዓላማና የተከፈለበትንም ዋጋ ዘንግተው የማይገቡ ተግባራትን ሲፈፅሙ ይስተዋላል፡፡ እነዚህ ችግሮችም ሕዝቡ በየመድረኩ ለብዙ ጊዜያት ሳይፈቱ የቆዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንዲያነሳ እንዳደረገው ይናገራሉ፡፡

ሼህ መሀመድ ሸሪፍ ሀሰን የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳይ ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ሀገሪቱ ለብዙ ዓመታት የቆየ ተቻችሎ በሰላም አብሮ የመኖር እሴቷን በሚቃረን መልኩ አልፎ አልፎ የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ ለዚህም እንደ ዋነኛ መንስዔ የሚሆነው የዕውቀት ማነስ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት የሃይማኖትም ሆነ ሌሎች የእኩልነት መብቶች ባልተረጋገጡበት ዜጎች እርስሰ በእርስ ተከባብረውና ሰላማቸውን ጠብቀው ይኖሩ እንደነበር በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ብልጭ ድርግም የሚሉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄን ሽፋን ያደረጉ ፀረ-ሰላም ኩነቶች እየተፈጠሩ እንደሆነ በመግለፅ፤ የእነዚህ መነሻም የግል ፍላጎት፣ ግንዛቤ ጉድለት እንዲሁም ቀጣይ የሀገሪቱን ዕድገት የማይፈልጉ አንዳንድ የውጭ አካላት እጅም አለበት እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ቤተ-ክህነት የሰበካ ጉባዔ ማደራጃ መመሪያ ዋና ፀሐፊና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰላም አምባሳደር ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንደሚናገሩት የሰላም መሰረቶች ፍቅር፣ መከባበርና መቻቻል ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ሀገሪቱ የምትታወቅበትና ጠብቃ የቆየችው እሴት ነው፡፡ የቀድሞ አባቶች አኩሪ ገድሎች ሲወሳም ይህንኑ አስተምረውና ለመጪው ትውልድ ትተው አልፈዋል፡፡ ነገር ግን ግጭቶች የሉም ማለት ሳይሆን ከሀገር ውጪ ዘመቻም ሲመጣ የነበረውን ልዩነትና ጊዜያዊ ችግር ወደጎን በመተው በአንድነት ሀገሪቱን ለማስከበር ሰርተዋል፡፡ ሀገራዊ በሆነ አጀንዳ ላይ በጋራ በመሆን በተባበረ አንድነት ይሰሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

አሁን ላይ አልፎ አልፎ የሚታዩ ችግሮች ታሪክንና ባህልን ካለማወቅ፤ የቀደሙት አባቶች ታሪክ ካለማውሳት ዓለም አንድ መንደር እየሆነች በመምጣቷ እንዲሁም ዜጎች በሃይማኖት በሥነምግባር ተኮትኩቶ አለማደግ አባትን የማይሰማ ትውልድ እንዲፈጠር እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም ችግሮችን በተረጋጋ ሁኔታ አጢኖ በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ በማን አለብኝነት በመልካም አስተዳደር ጥያቄ ስም የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥሩ አካላት እየተበራከቱ መሆኑን ተናግረዋል።

መፍትሄዎች

የክብር አምባሳደሩ አቶ ምዑዝ እንደሚብራሩት፤ ችግሮቹን ለማቃለል መንግሥት የሃይማኖት አባቶችና ሕዝብ በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተሻለና በተደራጀ ሁኔታ ለመመከት ሕዝቡ የሚያሳቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ያቃለል ሥራ መሥራት ይኖርበታል፡፡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ቦታ ላይ የሚቀመጡ አካላትም አብሮ በማምሸት፣ በመተዋወቅና ዝምድና መሠረት ያደረገ ሳይሆን ሥራን ማዕከል ባደረገ መልኩ ሲሆን ሀገሪቱ በሚፈለገው ደረጃ ሰላማዊና ልማታዊ ዕደገቷም በምቹ መደላደል ላይ የቆመ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡ ለዚህም «መንግሥት መጀመሪያ የራሱን ሰዎች መፈተሽ አለበት» ሲሉ ይናገራሉ፡፡

በሌላ በኩል ወይዘሪት ሕይወት በበኩላቸው፤ ችግሮቹን ለማቃለል ረጋ ብሎ መወያየትና መድረኮችን መፍጠር አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ምክንያቱም አልተስተካከሉም ብሎ የተስተካከሉ ነገሮችን ማጥፋት ውድመት እንጂ ልማት አይሆንም፡፡ አልተስተካከለም ተብሎ የሚታሰብ ችግርንም ለማስተካከል መረባረብ እንጂ የሆነ ጉዳይ አልተስማማኝምና የተስማማኝንም አጠፋለሁ ማለት የተሳሳተ አስተሳሰብ እንዲሁም ያለማሰብና ጤናማ አእምሮ ውጤት አለመሆን ነው የተናገሩት።

በምድር ላይ ብዙ የማያስማሙ ነገሮች አሉ፡፡ ይህም የተፈጠረው የሰው ልጆች አፈጣጠር መለያየት በራሱ የተለያየ ሰዎች ሁሌም በተለያየ መንገድ ስለሚያስቡ ነው:: ይሄን ልዩነት አንዱ ላንዱ በመሙላት በመልካም ጎኑ መጠቀም ከተቻለ የተሻሉ ለስኬት የሚበቁ ተግባራትን ማከናወን ይቻላል፡፡ «ሁላችንም መሪዎች ልንሆን አንችልም ነገር ግን ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ለሀገሪቱ መልካምነት የራሳችንን ድርሻ ማበርከት እንችላለን» በማለት ችግሮችን በሰከነ መልኩ መፍታት እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡

ወጣት ብሩክ በበኩሉ ወደ ጥፋት የሚያመሩ ገፆችን ገልጦ መመልከት ለችግሮቹ መፍትሄ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ ይህ ሲሆንም ለውጦች ማምጣት ይቻላል፡፡ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣትም መናገር ብቻ ሳይሆን ተግባር ላይ ማተኮር ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ ይህ መሆን ሲችል ወጣቱ ከመንግሥት ጋር በመሆን ሀገራዊ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ መፍትሄና ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡

ወይዘሪት መሠረት ለችግሮቹ መፍትሄ ናቸው ያሏቸውን ይናገራሉ። መንግሥት አስፈፃሚና ፈፃሚ አካላት ከሕዝቡ ጋር በመሆን ሊያንገዋልላቸው ይገባል፡፡ ኅብረተሰቡ ያሉ ልዩነቶችን መሠረት ባደረገ መልኩ መቻቻል ሊኖረውና ሰላሙን አስጠብቆ መቆየት ይገባዋል፡፡ ይህችን ሰላም ለማድፍረስ የሚራወጡ በቁጥር አነስተኛ ግለሰቦችን ወደ ሰላም ለማምጣት በሰላማዊና ፍቅር በተሞላበት መንገድ መሰራት ይኖርበታል፡፡

ጦርነት ለማንም የሚበጅ አለመሆኑን ማሳያ የሚሆነው በአሁኑ ወቅት የመጣው ለውጥ ነው፡፡ ይህንንም እድገት ቀጣይ ለማድረግ ሕዝብ ትግል ማድረግ ይገባዋል፡፡ በሌላ በኩል የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ የተቀመጡ ግለሰቦች የዘልማድ መሪዎች ሳይሆን እውነተኛ ሕዝባዊነት የተላበሱና ሰላሙን ቀጣይነት ለህዝቡ ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ማስጠበቅ አለባቸው፡፡ በዚህም ኃላፊዎች በየወሩ የሚቀበሉትን ደመወዝ ሳይሆን እውነትን መሠረት አድርጎ ቢሰሩ መልካም ነው ይላሉ፡፡

ኃላፊዎች ያስቀመጣቸውን ሕዝብ ማዳመጥና ሕዝብን ያላዳመጠ የትም እንደማይደርስ ማወቅ ይገባቸዋል፡፡ በተለያዩ የአመራር እርከኖች ላይ ያሉ አካላትና ፈፃሚዎች መልካም አስተዳደርን ከመድረክ ወሬነት ባለፈ በሥራ ሊያሳዩ ይገባል፡፡ የተቀመጡበትን ወንበርና ሥልጣን ላይ ያወጣቸውን ሕዝብ ማክበር አለባቸው፡፡ በተቻለ መጠንም የውሳኔ ሰው በመሆን በተግባር ማሳየት ቢችሉ የተሻለ ይሆናል፡፡ የሚስተዋለው የቸልተኝነት ጉዳይም ወደ ጎን በመተው ሕዝቡን እንደራሳቸው የሚያዩና ቅድሚያ የሚሰጡ መሆን ካልቻሉ አደጋው የከፋ ይሆናል። ምክንያቱም ሕዝብን ያላዳመጠ የትም አይደርስምና ሲሉ ያሳስባሉ፡፡

ሕዝቡም ነገሮችን በመልካም መተርጎምና በጉልበት ሳይሆን ሰላማዊ በሆነ መልኩ እውነትን መጋፈጥና ሰላማዊ ትግል ማድረግ አለበት፡፡ መልካም አስተዳደር ለማስፈን በሁካታ ሳይሆን ሁሉም የሀገሪቱ እንቅስቃሴ ላይ በያገባኛልና በባለቤትነት ስሜት በመነጋገር መሆን አለበት፡፡ «ዓለም የቀናብን ሰላምስ ስለምን ይደፈርሳልበማለት ይጠይቃሉ፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ አንድ በመሆኑ ይህን ባማከለ ሁኔታ ሰላሙን አስጠብቆ መሄድ ላይ ትኩረት መስጠት አለበት፡፡ ስለሆነም ሕዝብም መንግሥትን መደገፍና ከጎኑ መቆም መንግሥትም ሕዝብን ማዳመጥና በጋራ ሀገራዊ አጀንዳዎችን ለማሳካት ርብርብ ማድረግ ይገባል ፡፡

ሼህ መሀመድ ሸሪፍ ሀሰን መፍትሄ የሚሉትን ሀሳብ ሲያብራሩ፤ በተለይም በአሁኑ ወቅት ያለው ወጣት ኃይል በሀገሪቱ በተፈጠረው የዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ የመጣ በመሆኑ ስለ ሰላም ጠንቅቆ ማወቅ ይጠበቅበታል። ዘብ መቆምም አለበት፡፡

ችግሮቹን ለማቃለልም የሃይማኖት አባቶች በየተቋማቱ ስለ ሰላም ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች ይህችን የተከበረች ሀገር የመጠበቅ የማስጠበቅና የማስተማር ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህንንም የሃይማኖት መሪዎች የወሰድነው አቋም ነው እንቀጥልበታለን፡፡ መንግሥት ብቻ ሀገር አይጠ ብቅም፤ ሁሉም መረባረብ ይደኖርበታል፡፡ መንግ ሥትም ጉዳዩ ሀገራዊ በመሆኑ የሃይማኖት ተቋማትን በመደገፍ እንዲሁም በየዘርፉ ያሉ የሥራ ኃላፊዎችና ፈፃሚ አካላት ከኅብረተሰቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ በአግባቡ እየፈቱ መሄድ የሚችሉበትን ቁመና እንዲይዙ ማጠናከር አለበት ሲሉ ሼህ መሀመድ ያሳስባሉ፡፡

ችግሮቹን ለማቃለል መንግሥት ከሚመለ ከታቸው አካላት ጋር በመሆን በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡ በተመሳሳይ የሃይማኖት አባቶችም እዚህ ላይ ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ፡፡ በቀጣይ በቅዱስ ፓትርያርኩና ቅዱስ ሲኖዶስ የሚመራም ብዙ ሥራዎችን ለማከናወን ታቅዶ ወደ ተግባር እየተገባ ነው፡፡ በጉዳዩ ዙሪያም ሕዝቡን የማረጋጋት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህም የሕዝቡን ጥያቄ ለመንግሥት የማቅረብ መንግሥትም ያሉትን ችግሮች ለቅሞ በመያዝ ከኅብረተሰቡ ጋር የመፍታትና የማወያየት ሥራ እየተሰራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

በተለያዩ ወቅቶች ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ በመሆኑም ሀገሪቱ የጋራ በመሆኗ ችግሮች እንኳ ቢኖሩ በመወያየት፣ ጥያቄን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ቤት በማፍረስ ፣ መኪና በማቃጠልና እየመጣ ያለውን ለውጥ በማደናቀፍ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ አይችልም፡፡ በዚህ ልማት ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ባለው ድህነት ላይ እየታዩ ያሉ ብልጭታዎች ከቀጠሉ አስጊ ናቸውና ሁሉም ሰላምን ጠንቅቆ ሊጠብቅ ይገባል። በማለት ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ማጠቃለያ

የቀድሞ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ እንደሚናገሩት፣ የሰላም መጥፋትና መኖር ያለው በሰዎች አዕምሮ ላይ ነው፡፡ ሰዎች መልካም ነገር ማሰብ ሲችሉ በሀገር ያለው ሰላም የተጠበቀና ችግሮች እንዲቃለሉ ያስችላል፡፡ ከጦርነት ከሰላም ማጣት አንዳች የሚገኝ ትርፍ የለምና እያንዳንዱ የሀገሪቱ ዜጋ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በመነጋገር ለመፍታት መስራት ላይ ማተኮር አማራጭ የሌለው በመሆኑ ሁሉም መረባረብ እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

ፍዮሪ ተወልደ

Published in ፖለቲካ

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የሚያስገነባው የብዕር አምባ ዲዛይን፤

 

ዜና ሐተታ

በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት አዳራሽ በነበረው ኪነ-ጥበባዊ መሰናዶ «የኢትዮጵያ ድርሰት ማኅበር» ተብሎ ነበር ሥራውን የጀመረው። በሂደት መጠሪያውን ወደ «የኢትዮጵያ ደራስያን አንድነት ማኅበር» ተቀየረ፡፡ የአሁኑን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የሚለውን መጠሪያውን ያገኘው የካቲት 12 ቀን 1978 .ም ነበር፡፡

ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት፣ ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፣ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ፣ ጸሐፌ ተውኔት መንግስቱ ለማ፣ አቤ ጉበኛ፣ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን፣ ለማ ፈይሳ፣ ከበደ ሚካኤል እና ጳውሎስ ኞኞ የመሳሰሉት ማኅበሩን ካቋቋሙት ደራስያን መካከልም በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። ማሕበሩ ሲመሠረት በዋናነት ዓላማው አድርጎ የተነሣው በሀገሪቷ ያሉት የጽሑፍ ቅርሶች ተሰባስበው እንዲታተሙና ሌሎች አዳዲስ ጸሐፍትን ለማፍራት ነበር።

የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የሥራ ዘመኑ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል። በገንዘብ አቅሙ የጠነከረ ስላልነበር በተለያዩ ጊዜያት የሥራ ክንውኑን ጠንካራ እንዳልነበር ይነገራል። በአንድ ወቅት የአባላቱ ቁጥር ማነስና የገቢ ምንጮቹ መዳከም የጽሕፈት ቤቱን የቤት ኪራይ እንኳን ለመክፈል ተስኖት እንደነበርም አይዘነጋም።

1997 .ም አዲስ የሥራ አስፈፃሚ ቡድን ከመረጠ በኋላ ማኅበሩ በእጅጉ እየተቀየረ መጥቷል። ለብዙ ዓመታት በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የነበረውን ጽሕፈት በክልል ከተሞችም አስፋፍቷል፡፡ የገቢ ምንጮቹንም በተለያየ መንገድ አሳድጓል። በርካታ መሰናክሎችንም አልፎ በ58ኛ ዓመቱ የራሱን «የብዕር አምባ» ለመመስረት ሰሞኑን የመሰረት ድንጋይ አስቀምጧል።

መስከረም 17ቀን 2010 .ም ረፋድ ላይ፤ ሲ ኤም ሲ ኮተቤ ሚካኤል ፊትለፊት አንድ ታሪካዊ ክንውን ስለመኖሩ በአካባቢው ያለው ሽር ጉድ ያሳብቃል። ነጫጭ ድንኳኖች ተደኩነዋል፡፡ መሃል ላይ የብሄር ብሄረሰቦች ሰንደቅ አላማዎች ይውለበለባሉ። ዳርና ዳር ደግሞ የአፍሪካ አገራት ሰንደቅ አላማዎች ከፍብለው በመውለብለብ ላይ ናቸው። የአፍሪካ አገራት ሰንደቅ አላማ መውለብለብ ጉዳዩ ከሀገር አልፎ አህጉራዊ አንድምታ እንደሚኖረው ለመረዳት አያዳግትም። ዕለቱ ለኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር «የብዕር አምባ» የተሰኘ የስነ ጽሑፍ ማዕከል የግንባታ መሰረት ድንጋይ የማስቀመጫ መርሐ ግብር ነበር። ህንፃው ሲጠናቀቅ የአፍሪካ ደራሲያን ማህበር መቀመጫ እንደሚሆንም ተስፋ ተጥሎበታል።

የመሰረት ድንጋዩን የደራሲያን ማህበር መስራችና ዓቃቢ ነዋይ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሒሩት ወልደማርያም፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ያለው አባተና የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙሴ ያዕቆብ በጋራ አስቀምጠዋል።

በዕለቱ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙሴ ያዕቆብ የብዕር አምባው የኢትዮጵያ ደራሲያን መቀመጫ ብቻ ሳይሆን የብሄር ብሄረሰቦች የሥነጽሑፍ ትውፊታቸው የሚገለጥበት፣ የአፍሪካ ደራሲያን መቀመጫና የኢትዮጵያን ህዝቦችና አፍሪካን የሚወክል የቱሪስት መስህብ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ ወጪው ከ80 እስከ 100 ሚሊዮን እንደሚደርስ ተገምቷል፡፡ ይህን ገንዘብ ከማህበሩ ማግኘት ከባድ ቢሆንም መሰረቱ መጣሉ ብቻ ትልቁ ሥራ እንደተሰራ ቆጥረውታል፡፡

በከፍተኛ ዕድገት ላይ የሚገኙት ባንኮች ከሚገኝ ብድር፤ የክልል መንግሥታት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ ዩኔስኮንና ሌሎች ባለሀብቶችን በማሳተፍ ለመስራት አቅደዋል፡፡ ከመንግሥትም ድጋፍ ይጠበቃል፡፡ ግንባታው ሦስት ዓመታት እንደሚጠናቀቅ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ የብዕር አምባው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ብቻ ባለመሆኑ ሌሎች የጥበብ ቤተሰቦችም እንዲደግፉት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም፤ «ለማህበራችሁ ሥራ ፍሬ እንደ ማዕዘን ድንጋይ ለሚቆጠረው ለደራሲያንና የጥብብ ሰዎች መታሰቢያ ለሚሆነው የብዕር አምባ ህንጻ ግንባታ መሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ቀን በመድረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ፡» በማለት ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት።

«የቀደሙ አባቶች ቀለማቸውን ከብዕራቸው ላይ ሲያሰፍሩ የነበረው መንፈሳዊ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን ፍልስፍናቸውን፣ የስነ ፈለግና የፈውስ መድሃኒት ምርምራቸውን፣ የህዝባቸውንና በየዘመኑ የተነሱ ነገስታት ታሪኮች፣ የአገራቸውን ውበትና የህዝባቸውን ፍቅር ጭምር ነው። በመሆኑም በሥነፅሁፍ የሀገራችንን ምስጢር ለመፍታት ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ልጆቻችን የሀገራቸውን ምስጢራትና ታሪክ እንዲያውቁና እንዲመረምሩ ከማድረግ ይልቅ የባዕዳን ታሪክ እንዲያውቁ እያደረግናቸው ነው፡፡ የባዕዳኑን ልሳን ማወቃቸው ባይከፋም 'የሰው ወርቅ አያደምቅ' ነውና የራሳቸውን እረስተው በእጃችን ላይ እያሉ የሌላ ሆነው እንዳናገኛቸው ትልቅ ሥራ መስራት ይኖርብናል» ብለዋል። በዚህ ጉዳይ የደራሲያን ማህበር ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም መስክረዋል፡፡

«የሀገራችን የሥነጽሁፍ ዘርፍ እምርታዊ ለውጥ እንዲያመጣና የአፍሪካ ኩራት ይሆናል ብለን የምንተማመንበት ኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ግምባር ቀደም ነው» ያሉት ሚኒስትሯ፤ ማህበሩ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሁፍ ማደግ በርካታ ቁምነገሮችን ሲሰራ ቆይቷል። ወደፊትም በርካታ ፈተናዎችን እንደሚጠብቁት ተገንዝቦ ችግሮቹን በማሸነፍ ቀደምት አባቶቻችንን አሻራ እንደገና እንዲያንሰራራ ማድረግ እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡

ማህበሩ ባለፉት ዓመታት የንባብ ባህል እንዲያዳብር ያደረገው ጥረት የሚያስመሰግነው በመሆኑ ሰኔ 30 በሀገር አቀፍ ደረጃ የንባብ ቀን ሆኖ እንዲከበር የሚያደርገውን ጥረት ለመደግፍ ቃል ገብተዋል፡፡

«አሁን የመሰረት ድንጋይ የሚቀመጥለት የብዕር አምባም ሀገራችን የአፍሪካ ሥነ ጽሁፍ መቀመጫ እንድትሆን የሚያስችል በመሆኑ በርትተን በመስራት ለመጪው ትውልድ አኩሪ ታሪክ ልናሳርፍ ይገባል፡፡ ሚኒስቴሩም ከተሰጡት ተግባራት ዋናው በመሆኑ ህንፃው እውን ሆኖ ለሀገር በቀል ጥበባት የልህቀት ማዕከል እንዲሆን የበኩላችንን ጥረት ማድረግ አለብን» ብለዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ያለው አባተ በበኩላቸው፤ «አንድ ማህበረሰብ ስልጣኔዎች ከሚገለጹባቸው ጉዳዮች መካከል ባህልና ታሪካቸውን የሚያሰፍሩበት የሥነጽሁፍ ሀብቶቻቸው ናቸው። ኢትዮጵያም የምትታወቀው በብዝህነቷ ነው፡፡ ይህ የብዕር አምባ ብዝህነትን ወደአደባባይ ለማውጣት መልካም አጋጣሚ በመሆኑ የማዕከሉ መገንባት ለኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ልዩ ትርጉም አለው፡፡ በመሆኑም ፌዴሬሽን ምክርቤት ታላቅ አክብሮት አለው» በማለት የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

«በአሁኑ ወቅት ግሎባላይዜሽን የአፍሪካን ባህል እየፈተነው ነው፡፡ በመሆኑም በባህልና ጥበብ ላይ ብዙ መስራት ይገባል፡፡ የአፍሪካ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ ላይ አፍሪካ ደራሲያን ማህበር መቀመጫ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ቀጣዩ ትውልድ በተጠና እውቀት ላይ የተመሰረተ መረጃ ሊኖረው ይገባል። ህዝቦችን ባህልና ቋንቋ በማስረፅ በማንነቱ የሚኮራ ትውልድ እንዲፈጠር ከደራሲዎች ብዙ ሥራ ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም የብዕር አምባው ያስፈልጋቸዋል። በስነፅሁፋችን ላይ የሚመራመሩና ፈር የሚያሲዙ ወጣቶች ሊሰለጥኑበት ይገባል፡፡ መላው ህብረተሰብም ከጎናቸው ሊቆም ይገባል፡፡ መንግሥትም ተገቢውን እገዛ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ዲዛይኑን የሰራው ደራሲና አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው የብዕር አምባ ዲዛይን ለመስራት ዕድል በማግኘቱ «አርክቴክቸርንና ሊትሬቸርን» ለመተርጎም እንዳስቻለው ተናግሯል። ዲዛይኑ ጥንታዊውን መሰረት ይዞ ዘመናዊ በመሆኑ «አባቱን የሚመስል ልጅ» መሆኑን ነው የተናገረው፡፡ በውስጡም የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ጽሕፈት ቤት፣ ለአፍሪካ ደራሲያን ማህበር መቀመጫነት የሚሆን በቂ ቦታ ይዟል። የሥነጽሑፍ ሙዚየም፣ የድንጋይ ላይ ጽሁፎች፣ የብራና ጽሁፎች፣ ኢትዮጵያ ደራሲያን ሥነጽሑፎች በቅርስነት ተመዝግበው የሚቀመጡበትም ይሆናል፡፡

የመጀመሪያዋን ፊደል በመሮ ድንጋይ ላይ ቀረጾ ያስቀመጠው የማይታወቀው ደራሲ ሥራ በቅድሚያ ቦታ ይሰጠዋል። «እኛ ጀመርነው» በሚል ርዕስ ይስተናገዳል። የግቢው 55 በመቶ ለአረንጓዴ ቦታ የተተወ ነው። አካባቢው እንደ ደራሲያን ገዳም እንዲቆጠር ታስቧል፡፡ ደራሲያን መጥተው የሚያርፉበት፣ ከወጣት ጸሀፍት ጋር የሚወያዩበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

የስነቃል ሀብቶቻችንን የሚሰባሰቡበት ቤተመጻሕፍት ይኖረዋል፡፡ አፍሪካውያን ፀሀፍት ድርሰቶች የሚሰባሰቡበት ቤተ መጻሕፍት፤ የአካል ጉዳተኞችና የህጻናት ቤተመጻሕፍት ይኖሩታል። ደራሲያን እንደገዳም ዘግተው ድርሰቶቻቸውን የሚጽፉበት የእንግዳ ማረፊያንም አካቷል። የቴአትርና የፊልም ማሳያ አዳራሾች፤ እንዲሁም ትልቁ የደራሲ ራስምታት የሆነው የማተሚያ ቤት እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡ ሁሉም የጥበብ ሰዎች የሚታደሙበትና ልዩልዩ የንግድ ቦታዎች ይኖሩታል፡፡

 

ዳንኤል ወልደኪዳን

Published in የሀገር ውስጥ

በኢትዮጵያ ያለው የቆዳ ውጤቶች ምርት በዋጋ ደረጃ ከፍተኛ ነው። ነገር ግን የቆዳ እና ሌጦ ምርቶች ዋጋ እና ጥራት ደግሞ ዝቅተኛ መሆኑ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል። ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን ምን መደረግ አለበት? እስካሁንስ ያጋጠሙት ችግሮች ምንድን ናቸው? የሚመለከታቸውን የዘርፉ ተዋናዮችን አነጋግረናል።

የቆዳ ነጋዴው አቶ አብራር አሊ፤ በአሁን የቆዳና ሌጦ ዋጋ ከሁለት ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በአዲስ አበባ ከግማሽ በታች በሆነ ዋጋ እየተሸጠ ይገኛል። የበሬ ቆዳ በ30 ብር፣ የበግና ፍየል ሌጦ ደግሞ በ30 እና በ15 ብር እየቀረቡ ነው። ሆኖም አብዛኛው የአገሪቷ ኅብረተሰብ ከእርድ በኋላ የሚገኘውን ቆዳ ያለአግባብ በመያዝ ይጥለዋል ወይም ለቤት አገልግሎት ያውለዋል።

ለሽያጭ የሚቀርበውም ቆዳ እና ሌጦ ጥራቱ የወረደ በመሆኑ አብዛኛዎቹ ፋብሪካዎችና ተረካቢዎች አንቀበልም በማለታቸው በየጊዜው ቆዳ ነጋዴዎች ላይ ኪሳራ ይደርሳል። በመሆኑም ችግሩ የአገር መሆኑን በመረዳት ለጥራት የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። በማለት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ይናገራሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የቆዳ ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል ተጠባባቂ ሊቀመንበር አቶ አንተነህ ጌትነት እንደሚገልጹት፤ ቆዳውን ለማዘጋጀት የሚያገለግሉ ግብአቶች ዋጋ ከፍተኛ በመሆናቸው የምርት ውጤቶቹ ዋጋ ይጨምራሉ። የአገር ውስጥ ቆዳ ለማለስለስ እና ለምርት ዝግጁ እንዲሆኑ ለማድረግ በፋብሪካዎች ውስጥ የሚያስፈልጉ ኬሚካሎች ከውጭ አገራት የሚገቡ ናቸው። ኬሚካሎቹም በዋጋ ደረጃ ውድ ከመሆናቸው የተነሳ ፋብሪካዎቹ ወጪ ይጨምራሉ። የኬሚካል ዋጋ በጨመረ ቁጥር ደግሞ በቆዳ የሚሰሩ የተለያዩ ምርቶች ላይ ጭማሪ እንዲኖር ጫና ያደርጋል።

እንደ አቶ አንተነህ ገለጻ፤ በአገር ውስጥ ያለው የቆዳ እና ሌጦ ውጤቶች ለኢንዱስትሪው አመቺ አይደሉም። በተለይም እንስሳቱ በሕይወት እያሉ ቆዳቸው በበሽታ ስለሚጠቃ የቆዳው ጥራት በከፍተኛ ሁኔታ ይወርዳል። በተጨማሪም ለእርሻ አገልግሎት የሚውሉ እንስሳት በጅራፍ ተገርፈው እና በሥራ ጫና የተነሳ ቆዳቸው ተጎድቶ ስለሚታረዱ የቆዳው ጥራት አነስተኛ እንዲሆን ያደርገዋል። በዓይን የማይታዩ የቆዳ እና ሌጦ ችግሮችም በፋብሪካ ማቀነባበሪያዎች ውስጥ ሲገቡ እና በኬሚካል ጋር ሲደባለቁ ችግራቸው ጎልቶ ስለሚታይ ጥራቱን ከፍ ለማድረግ ደግሞ የሚያስፈልገው የኬሚካል መጠን እና ዓይነት እንዲጨምር ያስገድዳል።

የኬሚካል መጠን እና ዓይነት ሲጨመር ደግሞ ተጨማሪ ወጪ በመሆኑ ምርቶች ላይ የዋጋ መናር ያስከትላል። ይህ ሁሉ ተደማምሮ ከቆዳ እና ሌጦ ጥሬ ምርት ዋጋ ጋር በማይነጻጸር መልኩ የቆዳ ውጤቶች ዋጋ በእጅጉ ያሻቀበ እንዲሆን አድርጎታል።

በተጨማሪም ጥራቱ በተጓደለ ቆዳ የተነሳ በፋብሪካዎቹ ውስጥ የሚባክነው ምርት የኢኮኖሚ ጉዳት እንዳያደርስ እና ፋብሪካዎቹ የሚደርሰውን ኪሳራ ለማካካስ ያላቸው ዕድል የተሻለ ጥራት ያሳዩ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ነው። በመሆኑም ከኬሚካሎቹ ውድነት ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የምርት ዋጋ መጨመርን ለማውረድ የኬሚካል ማምረቻዎቹን በአገር ውስጥ መገንባት ያስፈልጋል። የፋብሪካዎቹ አገር ውስጥ መከፈት የኬሚካል ጥሬ ዕቃዎችንም ከአገር ውስጥ ለማዘጋጀት ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ በተሻለ ዋጋ ለቆዳ ማቀነባበሪያዎች ለማቅረብ ይረዳል። የዋጋ ሁኔታው የተያያዘ በመሆኑ እስከ ቆዳ ምርት ውጤቶች ድረስ የዋጋ ማሻቀብን የመቀነስ ዕድል አለው።

የኢትዮጵያ እንስሳት ቆዳዎች ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸሩ የተለየ ባህሪ አላቸው የሚሉት አቶ አንተነህ፤ በግ እና ፍየል ቆዳ ለጓንት ተመራጭ መሆኑን ይናገራሉ። በተለይ ወደ ጣሊያን እና የተለያዩ አውሮፓ አገራት የሚላኩ የቆዳ ጓንቶች ካላቸው ጥንካሬ የተነሳ ተመራጭነታቸው ከፍተኛ ሆኗል። በኢትዮጵያ የሚገኙ የበግ ዝርያዎች ቆዳ በአነስተኛ ስፋት እና ውፍረት ላይ ከፍተኛ ጥንካሬ የሚሰጥ ተፈጥሯዊ ባህሪ አለው። ከአፍሪካ ውስጥ ተመራጭ የሆነው የቆዳ ዓይነት የሚገኘው በኢትዮጵያ እና በናይጄሪያ ነው። በመሆኑም ይህን ዕድል አብዝቶ ለመጠቀም ከምርምር ጋር የተያያዙ ውጤቶችን በማስፋት በአግባቡ መስራት ያስፈልጋል።

በቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የቆዳ ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት አቶ ታዬ ጥበቡ እንደሚናገሩት፤ በኢትዮጵያ የቆዳ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የሚያቀርቡት ምርት በመካከለኛ እና አነስተኛ አምራቾች ዘንድ ተፈላጊ ሆኗል። በመሆኑም የቆዳ ምርት ውጤቶችን አቅራቢ ተቋማት እና ግለሰቦች የሚያቀርቡት ምርት ከአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ቢረከቡም ሁሉቱም አቅራቢ እና ተቀባይ አካላት ተጠቃሚዎች ናቸው። የቆዳ ምርቶች ዋጋ ማሻቀብ ቢኖርም የማምረቻ ዋጋ እና ቴክኖሎጂው የሚጠይቀው ሀብት ላይ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም የአገር ውስጥ ገቢው ለቆዳ ማቀነባበሪያዎች እና ለአምራቾች አዋጭ በመሆኑ ችግር እየተፈጠረ አይደለም።

ነገር ግን የቆዳ ማቀነባበሪያዎቹ ምርቶቹን ወደ ውጭ አገራት በሚያቀርቡበት ወቅት ተወዳዳሪነታቸው ላይ ችግር እየፈጠረ ይገኛል። ምክንያቱም የዓለም አቀፍ ገበያው ከፍተኛ ጥራት የሚፈልግ እና የአቅርቦት አቅምን መሠረት ያደረገ ነው። በመሆኑም የአገር ውስጥ ማቀነባበሪያዎች በዓለም አቀፍ ገበያ ሲቸገሩ ይስተዋላል።

በዚህ ምክንያት ትላልቅ የጫማ እና ጃኬት አምራቾች ከፍተኛ የቆዳ ምርት በሚፈልጉበት ወቅት ከዓለም አቀፍ አቅራቢዎች ላይ እንዲገዙ ይገደዳሉ። በመሆኑም በአገር ውስጥ ያሉት ከፍተኛ አቅም ያላቸው የቆዳ ጫማ፣ ቦርሳ እና ጃኬት አምራቾችም የሚፈልጉትን ቆዳ ምርት ለማቅረብ የአገር ውስጥ ማቀነባበሪያዎች በአቅርቦት አቅም እና በጥራት የተሻሉ ሆነው መቅረብ አለባቸው።

በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት ያለው ዕድል የቆዳ ጥራት እንዲጠበቅ እንስሳትን ከውልደታቸው ጀምሮ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ኅብረተሰቡን ማስተማር ያስፈልጋል። በተጨማሪም ለእንስሳት ጥበቃ ትኩረት በመስጠት በተለያዩ በሽታዎች የሚመጡ ጉዳቶችን ለመቀነስ ቆዳው ሳይጎዳ እንስሳት ህክምና የሚያገኙበት ልምድ ማስፋፋት ይገባል። ለቆዳ እና ሌጦ ምርት ጥራት የሚጨነቅ ማህበረሰብ ከተፈጠረ እና የተሻለ ይዘት ያላቸው ምርቶች ማቅረብ ከተቻለ ዘርፉ የተጋረጡበትን ፈተናዎች ማለፍ ይችላል።

የቆዳ ቴክኖሎጂ ባለሙያው ዶክተር ታደሰ ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ያለው የቆዳ እና ሌጦ ጥራት አቅራቢዎች ያለው ሰንሰለት የተበላሸ መሆኑን ይናገራሉ። በቀድሞ ጊዜ እንደ ወረዳ እና ቀበሌ ባሉ የአስተዳደር እርከኖች ላይ የሚመደብ የቆዳ ጥራት ተቆጣጣሪ ባለሙያ ጥራቱ ያልተጠበቀ ቆዳ ያቀረበ ግለሰብን እስከማሳሰር የሚደርስ ሥልጣን እንደነበረው ያስታውሳሉ። በአሁኑ ወቅት ግን ጉዳዩ በዋነኛነት የሚመለከተው የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ጭምር ጥራትን ለማስጠበቅ አቅም የለውም። ኢንስቲትዩቱ በአሁኑ ወቅት የቆዳ እና ሌጦ ጥራት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ «ጥርስ የሌለው አንበሳ» ሆኖ መታየቱን ይጠቁማሉ።

ኢንስቲትዩቱ በሰው ኃይል ቢደራጅም በአገሪቷ ጠረፍ አካባቢ ስለሚከናወነው የቆዳ ጥራት ማስጠበቅ ሥራ ለመከታተል ተገቢውን ትኩረት እየሰጠ አይደለም። የቆዳ ጥራት በወረደ ቁጥር ደግሞ የተሻለ ጥራት ያለው ምርት ለማግኘት የሚፈጀው ሀብት ከፍተኛ በመሆኑ የምርት ዋጋውን በዚያው ልክ ይጨምራል። በመሆኑም ኢንስቲትዩቱን አቅሙን በማጠናከር በመላ አገሪቷ ፍሬ ያለው ሥራ ሊያከናውን እንደሚገባ ይመክራሉ።

በሌላ በኩል የእንስሳት ቆዳን የሚያጠቃው የጥገኛ በሽታ ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት በመላ አገሪቷ የተቀናጀ አሠራር እየተተገበረ አለመሆኑን ይናገራሉ። በሽታውን በመከላከል እና ጥራቱ የተጠበቀ ቆዳ እና ሌጦ ከማቅረብ አንጻር አንደኛው ክልል የተሻለ ሥራ ሲያከናውን ሌሎች ደግሞ ዝቅተኛ አፈጻጸም ይታይባቸዋል። በመሆኑም በአገር አቀፍ ደረጃ በሽታውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት ያስፈልጋል።

የቆዳ ጥራት ከሚፈትኑ ጉዳዮች ዋነኛው የእንስሳት በሽታ መሆኑን የሚያስረዱት ዶክተር ታደሰ፤ ቆዳ ለፋብሪካዎች በሚቀርብበት ወቅት በዓይን የማይታዩ ችግሮች ከማቀነባበሪያው ሂደት በኋላ በጉልህ እንደሚታዩ ይጠቁማሉ። በመሆኑም ደህና ቆዳ ነው የተባለው በፋብሪካ ውስጥ በጀርሞች እና በተለያዩ ፓራሳይቶች የተጠቃ ሆኖ ሲገኝ ለፋብሪካዎቹ ምርታማነት አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል።

ችግሩ እየሰፋ በመሄዱ ደግሞ ፋብሪካዎች በብዛት እና በጥራት በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት እንዳያቀርቡ እያገዳቸው ነው። መንግሥትም የተሻለ ዋጋ የሚያስገኙ ያለቀላቸው ምርቶች እንዲላኩ ግብ ከማስቀመጡ ጋር ተያይዞ ጥሬ ቆዳ እና ሌጦ ወደ ውጭ አገራት እንዳይላክ ክልከላ መደረጉ ይታወሳል። በመሆኑም ያለቀላቸውን ምርቶች በጥራት እና በብዛት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ እያንዳንዱ ግለሰብ የእራሱን አስተዋጽኦ በእንስሳት ጥበቃ ላይ ሊያደርግ እንደሚገባ ነው የሚያስረዱት።

 

ጌትነት ተስፋማርያም

Published in ኢኮኖሚ

የቻይና ቱሪስቶች ኢትዮጵያን ቀዳሚ ምርጫ አድርገዋል፤

 

ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እያከናወነች ያለውን ስኬታማ ተግባራት የተለያዩ ዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙኃን በድረገጾቻቸው ለንባብ አብቅተዋል። በተለይም በኢኮኖሚው መስክ እየታየ ያለው ለውጥ፣ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በማከናወን ላይ ያሉት ተግባራት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው ለመውጣት የሚያስችላቸውን አቅጣጫ እንደያዙ ዘገባዎቹ የዳሰሷቸው እውነታዎች ናቸው። ባለፈው ሳምንት መልካም ገጽታዎችን አጉልተው ካስነበቡት መካከል የሕንድ ፕሬዚዳንት የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ጉብኝታቸው በኢትዮጵያና ጅቡቲ እንደሚያድርጉ፤ኢትዮጵያ የቻይና ቱሪስቶችን በከፍተኛ ሁኔታ እየሳበች ስለመገኘቷ፤ የቻይና የፊልም አውደ ርእይ በኢትዮጵያ ስለመከፈቱና ሌሎችም ዘገባዎች ይገኙበታል፡፡

የሕንድ ፕሬዚዳንት የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያና ጅቡቲ ያደርጋሉ

የሕንድ ፕሬዚዳንት ራም ናት ኮቪንድ በመጪው ጥቅምት ወር የመጀመሪያው የውጭ አገር ጉዟቸው አካል የሆነው በኢትዮጵያና ጅቡቲ ጉብኝት ማድረግ እንደሚጀምሩ ፈረስት ፖስት ድረገጽ ጠቁሟል፡፡ ጉብኝታቸው ሕንድ በአፍሪካ ላይ መንቀሳቀስ በምትጀምርበት ወቅት በመሆኑ ልዩ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ለቻይና በአህጉሪቱ መስፋፋትም ምላሽ የሚሰጥ እንደሚሆን ድረገጹ ዘግቧል፡፡

አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫና ከ540 በላይ ለሚሆኑ የሕንድ ድርጅቶች መዳረሻ መሆኗ ሂንዱስታን ታይምስ ድረገጽ ጠቅሷል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ከሁለትዮሽ ምክክር ባሻገር ኢትዮጵያና ጅቡቲ ከሕንድ ጋር ያላቸው ልዩ ግንኙነትን እንደሚያጠናክር ይጠበቃል፡፡

ሕንድ በአፍሪካ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን የሚያስገኝላት ሲሆን፤ ከተወሰኑ የአፍሪካ አገራት ያላት ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነቷ ጤናማ ግንኙነትን ለመመስረት ይበልጥ ወሳኝ ነው፡፡ ሕንድ በተጨማሪ በአፍሪካ አገራት ዘላቂ ለሀገር ግንባታ አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ማቅረብ የምትችል አገር መሆኗ በአፍሪካ የሕንድ ምክር ቤት በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ጥናት ባለሙያ ሳንጄይ ፑሊፓካ ተናግረዋል፡፡ ባለፈው እአአ በ2015 በኒው ዴልሂ ከተማ የተደረገው የኢንዶ አፍሪካ ጉባኤ ከአፍሪካ ከ40 አገራት በላይ የተውጣጡ አመራሮች የተሳተፉበት መሆኑንም ድረገጹ አስታውሷል፡፡

(First post 28 September 2017)

ኢትዮጵያ የቻይና ቱሪስቶችን በከፍተኛ ሁኔታ እየሳበች ነው

በኢትዮጵያ የቻይና ጎብኚዎች በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል። እአአ በ2012 ከነበረው 35 383 የቻይናውያን ጎብኚዎች ቁጥር እአአ በ2015 ወደ 41 660 መድረሱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ባለሙያ አቶ ካሳሁን አያሌው ተናግረዋል፡፡

ባለሙያው ከቻይናው የመረጃ ምንጭ ዢንዋ ድረገፅ ባደረጉት ቆይታ ምንም እንኳ የቻይና ጎብኚዎች ከአሜሪካና እንግሊዝ ከሚመጡ ጎብኚዎች ጋር ባይመጣጠንም ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ግን ቻይናውያን ጎብኚዎች ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱና ለሀገሪቱ ከፍተኛ ገቢ እያስገኙ መሆናቸው ጠቁመዋል፡፡

በቻይናውያን ጎብኚዎች በተለይ በምግብ አያያዝ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ክፍተት መኖሩን የጠቆሙት ባለሙያው ይህን ለማስተካከል ግን ይበልጥ እየተሰራ መሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ እአአ 2016/17 ኢትዮጵያ ከ886 897 ጎብኚዎች 3 ነጥብ 32 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ተገልጿል፡፡

ሀገሪቱ እአአ በ2017/18 በጀት ዓመት ከ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ጎብኚዎች 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት አቅዳ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡ ቱሪዝም የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ ምንጭ ማድረግ በሚል መሪ ሃሳብ ኢትዮጵያ በቱሪዝምና ጎብኚዎች አያያዝ ኢንዱስትሪ ለሚንቀሳቀሱ የሥራ ንግድ ፈጣሪዎች ማበረታቻ እያደረገች መሆኗንም ዢንዋ ድረገጽ አስነብቧል፡፡

(Xinhua 29 September 2017)

የቻይና የፊልም አውደ ርእይ በኢትዮጵያ ተከፈተ

ዢንዋ ድረገጽ ይዞት በወጣ ዘገባው የቻይና የፊልም ኤግዚቪሽን በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ከተማ የቻይና የባህል ሳምንት አካል በመሆን መከፈቱን ዘግቧል፡፡ በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የባህል አማካሪ ያን ዢያንግዶንግ የመጀመሪያው የቻይና የፊልም ኤግዚቢሽን የቻይና ሕዝብ የረጅም ጊዜ ሥልጣኔ በኢትዮጵያ ለማሳየትና አኩሪ ሥልጣኔያቸውን ለማስተዋወቅ መሆኑ ተናግረዋል፡፡

አፍሪካ የቻይና ፊልም ኤግዚቢሽን የ2017 የቻይና ባህል ሳምንት በአዲስ አበባ አካል ሲሆን የባህል ሳምንቱ ሦስት ክፍል በማካተት አንዱ የጉዋንግዶንግ ግዛት አርት በብሔራዊ ጉዳትና በአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የሚያውጠነጥን ነው፡፡

በተጨማሪ የባህል አማካሪው ያን በኢትዮጵያ የሚታዩ አጠቃላዩ ስድስት ፊልሞች በኢትዮጵያ ያለው የቻይና ፊልሞች ከቴኳንዶ ጋር የተያያዙ በመሆናቸው የተሻለ ግንዛቤ የሚፈጥር ይሆናል ብለዋል፡፡ ቻይና ሰፊ አገር እንደመሆኗ መጠን ዓለም ከሚያውቃት የነ ብሩስ ሊና ጃኪ ቻን የቴኳንዶ ፊልሞች በላይ በርካታ ባህሎች እንዳሏት ለማሳየትና ለማስተዋወቅ ይረዳል ሲሉ አብራር ተዋል፡፡

(Xinhua 29 September 2017)

የሕንድ ካቢኔ የኢትዮጵያና ሕንድ የትብብር ስምምነት አጸደቀ

በጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የተመራው የሕንድ ካቢኔ አገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር በመረጃ፣ በኮሚዩኒኬሽን እና ሚዲያ ዘርፍ በጋራ እንዲሰሩ ለማስቻል የተዘጋጀውን የትብብር ስምምነት አፀደቀ።

ስምምነቱ የሁለቱ ሀገሮች በኢንፎርሜሽን፣ ኮሚዩኒኬሽን እና መገናኛ ብዙኃን ያላቸውን ግንኙነት ማጎልበት እና ማስፋፋት ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ የሁለቱም አገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠንከር እንደሚያግዝም ተገልጿል። በተጨማሪም ሁለቱም ሀገራት ምርጥ ልምዶችን እና አዳዲስ ፈጠራዎችን እንዲቀባበሉም ያስችላል ነው የተባለው።

ስምምነቱ እንደ ሬዲዮ፣ ህትመት ሚዲያ፣ ቴሌቪዥን እና ማህበራዊ ሚዲያን በመሰሉ የሚዲያ ዘርፎች የበለጠ ተባብረው እንዲሰሩ ያግዛቸዋል። በሁለቱ ሀገራት መካከል የሰው ኃይል ልውውጥ ለመፈፀም እንደሚሰራ ነው የተጠቆመው። የሕንድ መገናኛ ብዙኃን ስለ ኢትዮጵያ፤ የኢትዮጵያ አቻቸው ደግሞ ስለ ሕንድ አጠቃላይ ሁኔታ ለሕዝቦቻቸው መረጃ እንዲያደርሱም የሚያግዝ መሆኑን ኒውስ ከሬላ ዶት ኮም ድረገጽ አስታውቋል።

(newskerala.com 27 September 2017)

አጠቃላይ አገራዊ እድገት 9 በመቶ መሆኑ ተነገረ

የዓለም ገንዘብ ድርጅት በሚስተር ጁሊዮ ኢስኮላኖ የተመራ የልዑካን ቡድን እአአ የ2017 አራተኛው አርቲክል ከኢትዮጵያ ጋር የምክክር መድረክ እአአ ከመስከረም 13 እስከ 26 ቀን 2017 መካሄዱ ይታወቃል፡፡ ሚስተር ኢስኮላኖ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እአአ በ2016/17 የኢትዮጵያ ምርቶች በውጭ ገበያ ከነበራቸው ዝቅተኛ ዋጋና በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተከስቶ ከነበረው ድርቅ ባሻገር ጠንካራ እድገት ማሳየቱን ጠቅሰዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ አገራዊ ገቢም እስከ 9 በመቶ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ መንግሥት ከልማት ድርጅቶች ጋር በመተባበር በድርቅ የተጠቁ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የመርዳት እንቅስቃሴው ጊዜውን የጠበቀና በቂ መሆኑን መስክረዋል፡፡ አያይዘውም በወሳኝ ፕሮጀክቶች መወዳደር መዘግየትና ደካማ ዓለም አቀፍ የምርት ገበያ የኢትዮጵያ የውጭ ንግዱ መቀዛቀዝ እንደታየበት ጠቁመዋል፡፡

የመካከለኛ ጊዜ እድገት አመላካቾች በጣም አዋጪ ሲሆኑ በጠንካራ የግል ባለሀብቶች የታገዙ፣ ወሳኝ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በመጠናቀቅ ላይ ናቸው። እንዲሁም የውጭ ንግድ ትኩረት ያደረጉ ኢንዱስትሪዎች በመገንባት ላይ በመሆናቸው ምርታማነት ይጨምራል፡፡ በአንጻሩ የአጭር ጊዜ እድገቱ ሲታይ ግን አሁን ያለው የዋጋ ግሽበት ከፍተኛ በመሆኑ፣ የብድርና ተያያዥ አደጋዎች በመጨመራቸው እንደሚፈለገው አለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡ የገንዘብ ድርጅቱ ሠራተኞች በሀገሪቱ የተመዘገበው የፋይናንስ እድገትና ሁሉም አቀፍ መሆኑ በሀገሪቱ ያሉ የባንኮች ቅርንጫፎችና ቁጠባ መጨመር ዋና ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ አድናቆታቸው ገልጸዋል፡፡

አሁን በኢትዮጵያ አወንታዊ አመለካከት እያደረገ ያለው ባለሀብት የቢዝነስ ሁኔታው በማሻሻል ከፍ ማድረግ ይቻላል፡፡ ተለዋዋጭ የምንዛሬ መጠንም ቢሆን ተወዳዳሪነትን እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡ የምጣኔ ሀብት ስታትስቲክስ በማሻሻል የፖሊሲ አውጪዎችና ባለሀብቶች በራስ መተማመን መደገፍ ይቻላል፡፡ የቡድኑ አባላት ግኝታቸውና ምክራቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ያደረሱ ሲሆን፣ በቴክኒክና ፖሊሲ ዙሪያ ደግሞ ከብሔራዊ ባንክ አስተዳደርና የፋይናንስ ኢኮኖሚክ ትብብር ሚኒስትር ጋር መወያየታቸው አይ ኤም ኤፍ ድረገጽ ይፋ አድርጓል፡፡

(IMF 26 September 2017)

 

በሞኒተሪንግ ክፍል

Published in ዓለም አቀፍ
Monday, 02 October 2017 21:41

ፓርላማ - 2010 ዓ.ም

 

ከፍተኛ አገራዊና ሕዝባዊ ኃላፊነት ያለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2010 .ም የሥራ ዘመን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሊጀመር ጥቂት ቀናት ቀርተውታል። በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 58/2 ላይ እንደተቀመጠው የምክር ቤቱ የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እስከ ሰኔ 30 (ሰላሳ) ነው። በመካከሉም ምክር ቤቱ በሚወስነው ጊዜ የአንድ ወር እረፍት ይኖረዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ዘመኑ የሚሰራቸው ተግባራት እጅግ በጣም ብዙ ናቸው። ምክር ቤቱን የማይመለከት አንዳችም ሀገራዊ ጉዳይ የለም ለማት ይቻላል።

ዝርዝሩ በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 55 ስር ሰፍሯል። ጥቂቶቹን እነሆ... የመሬትና የተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ ወይም ከአንድ ክልል በላይ የሚያስተሳስሩ ወንዞችና ሐይቆች አጠቃቀምን የተመለከቱ የምክር ቤቱ ሥራዎች ናቸው። በክልሎች መካከል የሚኖረውን የንግድ ልውውጥና የውጭ የንግድ ግንኙነቶችን ይመለከታል። የአየር፣ የባቡር፣ የባህር መጓጓዣ፣ የፖስታና የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችንና አውራ መንገዶችን ይመለከታል። በሕገመንግሥቱ የተደነገጉትን የፖለቲካ መብቶች አፈፃፀምና ምርጫን የተመለከቱ ጉዳዮች የምክር ቤቱ ኃላፊነቶች ናቸው። የዜግነት መብት፣ የኢምግሬሽን የስፖርትና ወደ ሀገር የመግቢያና የመውጫ ጉዳዮች፤ የስደተኞችና የፖለቲካ ጥገኝነት ጉዳዮችን ይመለከታል። አንድ ወጥ የመጠን መለኪያ ደረጃና የጊዜ ቀመር የተመለከቱ ጉዳዮች፤ የጦር መሣሪያ ስለመያዝ፤ የሠራተኛ ሕግ ማውጣት፤ የንግድ ሕግ /ኮድ/ ማውጣት፤ የወንጀለኛ ሕግ ማውጣት፤ የፌደራል መንግሥት የሀገርና የሕዝብ መከላከያ ደህንነትና የፖሊስ ኃይል አደረጃጀትን መወሰን፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ/አንቀጽ 93/፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያቀርብለት የሕግ ረቂቅ መሠረት የጦርነት አዋጅ ማወጅ፤ ግብርና ታክስ መጣል፤ የመን ግሥት በጀት ማጽደቅ... ሌሎችም በርካታ ኃላፊነቶች አሉበት። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ሥራው የሚጀመረው በአዲሱ ዓመት መስከረም ወር የመጨረሻው ሰኞ ዕለት ነው። ይህም ሰኞ መስከረም 29 ቀን 2010 .ም መሆኑ ነው።

ፕሬዚዳንቱ የሚያደርጉት ንግግር የአገሪቱና የሕዝቡ አጠቃላይ የዓመቱ መመሪያ ነው። የአገሪቱን የእድገት ጉዞ አቅጣጫ የሚያሳይ መሪ ንግግር ነው። በዓመቱ ከሚያደርጉት በማንኛውም ደረጃ ከሚደረጉ ንግግሮች ሁሉ በላጭ ንግግር ነው። ለሌሎች ተናጋሪዎችም ሆነ ለመንግሥት የሥራ ዘርፎች እንደማገናዘቢያ የማዕዘን ራስ የሆነ ንግግር ነው። ታላቅ ንግግር እንደመሆኑ መጠን በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚዘጋጁ መሆኑ አያጠራጥርም። ብዙ አገራዊና ሕዝባዊ ቁምነገሮች ይካተቱበታል ተብሎ ይጠበቃል። በአንድ ወይም በሌላ አማርኛ/አገላለጽ/ የሚከተሉት ርዕሰ ጉዳዮች ቢኖሩበት ምኞታችን ነው።

1/ የፌደራል ሥርዓቱን ስለማስጠበቅ፡-

ሕገ መንግሥቱ የአገራችን መንግሥት ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አወቃቀርን የሚከተልና መጠሪያውም «የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ» የሚሰኝ መሆኑን በምዕራፍ አንድ አንቀጽ አንድ ላይ ደንግጓል። ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ መሆኑን ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከሕገመንግሥቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተቀባይነት እንደማይኖረው የሕገ መንግሥቱን የበላይነት በሚገልፀው አንቀጽ 9/ዘጠኝ/ ላይ ተቀምጧል። ማንኛውም ዜጋ የመንግሥት አካላት የፖለቲካ ድርጅቶች ሌሎች ማህበራትና ባለሥልጣኖቻቸው ሕገመንግሥቱን የማስከበርና ለሕገመንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት እንዳላቸውም ተደንግጓል። በማንኛውም መንገድ በሕገመን ግሥቱ የተደነገገውን የፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አወቃቀር ሥርዓት ማናጋት አይችልም። የፌደራል ሥርዓቱን መጠበቅና ማስጠበቅ ሕገመንግሥቱን ማክበርና ማስከበር ማለት ነው።

ምንም እንኳን ከፌደራል መንግስቱ አቅም ውጪ ባይሆንም በተወሰኑ አካባቢዎች በየምክንያቱ የሚነሱ ግጭቶች እየተስተዋሉ ነው። ግጭቶቹ የየራሳቸው መንስኤ ቢኖራቸውም ከሚያልቀውና ከሚፈናቀለው ሕዝብና ከሚወድመው ንብረት አንፃር ሲታይ በፌደራሊዝሙ አወቃቀር ምክንያት የተከሰቱ እስከሚመስሉ ድረስ ገዝፈዋል። ይህን ሁኔታ ማስተካከል አለብን። ፌደራሊዝሙ የግጭት መንስኤ ሰበብ ሊሆን እንደማይችል ለሕዝባችን ያለማቋረጥ ማሳወቅ አለብን። በክልሎች መካከል ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ቀድመን መሥራት አለብን።

ከተከሰቱም በኋላ ከክልሎች ፍቃድ ውጪም ቢሆን የፌደራል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ግጭቱን በማስቆም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። ክልሎች በራሳቸው ዘዴ «ያስቆሙታል» ተብሎ ጊዜ መውሰድ አያስፈልግም። በፌደራሊዝም ሰበብ የሚጣሰው ሕገ መንግሥቱ ስለሆነ ሕገ መንግሥቱን ለመጠበቅና ለማስከበር ማንኛውንም አማራጭ መጠቀም አለብን። በድንበር ሰበብም ሆነ በሕዝቦች የሕይወት መስተጋብር ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮች በሰላማዊና በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱና ግጭቶች እንዳይከሰቱ ከክልል መሪዎች አንስቶ በየደረጃው የሚገኙ ባለሥል ጣኖች ሕዝባዊና መንግሥታዊ ኃላፊነ ታቸውን መወጣት አለባቸው። በመንግሥት እይታ ውስጥም ሁሉም ክልሎች በእኩልነት መታየት አለባቸው። በግጭቱ ለደረሰው ጉዳይ እጅ ያለበት ሁሉ እኩል ተጠያቂ ሆኖ ፍትሐዊ ርምጃ ሊወሰድበት ይገባል። በቅርቡ በተነሳው የሁለቱ ክልሎች አካባቢዎች ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ልባዊ የህሊና ፀሎት በማድረግ ስብሰባው ቢከፈት በእጅጉ የሚደገፍ ነው።

2. የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ማጠናከር፡-

የመንግሥታችን አወቃቀር መጠሪያ/ስያሜ/ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ነው። በመሆኑም የፌደራል ሥርዓቱን ከመጠበቅ ጐን ለጐን የዴሞክራሲ ሥርዓቱን አጠናክሮ ማስቀጠል ወሳኝ ነው። ይህም ሲባል የፖለቲካ ምህዳሩ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በሰፊው ማንሸራሸር እንዲችል ማድረግን ይጨምራል። ፓርቲዎች በምርጫ ወንበር እንዲያገኙ የሚያስችል አቅም እንዲያበጁ ማድረግ በአብዛኛው አቋማቸው ተመሳሳይ የሆኑ ፓርቲዎች በመካከላቸው ያሉትን ልዩነቶች በማቻቻል ህልውናቸውን ሳይለቁ ግንባር ፈጥረው እንዲታገሉ መደገፍ የምርጫ ሜዳውና ሂደቱ ግልጽና ተአማኒ እንዲሆን ማድረግ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በየራሳቸው ዓላማ ዙሪያ ያሰለፉት የሕዝብ ክፍል ስላላቸውና የሕዝብን ፍላጎት የሚያንፀባርቁበት የፓርላማ መድረክ (ወንበር) የሚያገኙበትን አካሄድ ተግባራዊ ማድረግ፣ ከሕዝብ ጋር የሚገናኙበትና ዓላማቸውን ለሕዝብ ተደራሽ የሚያደርጉበት የሚዲያ ተደራሽነት ዕድል እንዲያገኙ ወይም የየራሳቸውን ጋዜጣ/መጽሔት አዘጋጅተው ማሰራጭት የሚችሉበት አግባብ እንዲኖር፣ የጽሕፈት ቤትና የመሰብሰቢያ ቦታ እንዲያገኙ ተከታዮቻቸውን ሰላማዊ ሰልፍ የሚጠሩበት መደበኛ አሠራር እንዲኖር ማድረግ አለብን።

እስካሁን «አውራው ፓርቲ ጋር» ለመደራደር ፈቃደኛ ከሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እየተደረጉ ያሉ ውይይቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከሩና እያግባቡ መሆናቸውን አውቀናል። በዚሁ እንዲቀጥልም የሕዝባችን ፍላጐት ነው። ከዚህም አልፎ በየራሳቸው ምክንያት ያልመጡ ቡድኖች ወደ ፓርቲዎች መድረክ እንዲመጡ ጥረት ቢደረግ መልካም ነው። በእርግጥ «አልፈልም» ያለን ቡድን በግድ ጐትቶ ማምጣት አይቻልም። እምቢ ካለ ምንም ማድረግ አይቻልም። ይሁን እንጂ በራሳቸው መንገድ በሰላማዊ ዘዴ ለመታገል ያላቸውን መብት እንዲጠቀሙ ማገዝ የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ለማጠናከር ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው።

የዴሞክራሲያዊ አሠራር ሂደታችን ችግር ካለበት የፌደራላዊ ሥርዓቱም ለችግር ተጋላጭ እንዳይሆን የዴሞክራሲ አካሄዳችንን እያሰፋን መጠቀል አለብን።

3. የሥርዓቱ አደጋዎች ላይ በቁርጠኝነት መሥራት፡-

ሁሉም የሥርዓቱ አደጋዎች አገራችንን ለውድቀት የሚዳርጉ ቢሆኑም በተለይ የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ጡንቻው እየፈረጠመ መጥቷል። የመልካም አስተዳደር ጉድለታችንን ቀዳዳ እያሰፋ፤ በአገልግሎት አሰጣጥ ተገልጋዩን ሕዝብ እያስከፋ፤ የሀገሪቱን ሀብት እኩል ተጠቃሚነት መርህ እያዛባ መቀጠሉ አልበቃ ብሎት በሕዝቦች መካከል የእርስ በርስ ጥላቻ እንዲነግስ፤ በወስን ጉዳይና በሌሎችም ሰበቦች ሕዝብ እንዲጫረስ፤ ሕይወት እንዲጠፋና ከቀየው እንዲፈናቀል ወደሚያደርጉ ደም አፍሳሽ ሂደቶች ውስጥ እንድንገባ እያደረገን ነው።

በሰሞኑ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልለ አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውና ከፍተኛ ጉዳትን ያስከተለው ግጭትም በዋነኛነት የወሰን ጉዳይና የሕዝቦች አለመግባባት ውጤት ሳይሆን የኪራይ ሰብሳቢነት ያስከተለው መዘዝ ነው። በኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካ ኢኮኖሚ ላይ በፅናትና በቁርጠኝነት መሥራት ከመንግሥትም ከሕዝብም ይጠበቃል። ጠባብነትና ትምክህተኝነትም በእኩል መጠን ሊወገዙ የሚገባ ችግሮች ቢሆኑም ኪራይ ሰብሳቢነት ሲጨመርባቸው ደግሞ የሀገራችንን ሁኔታ ይበልጥ ውስብስብ ያደርጉታል። በሕዝቦች መካከል በክልሎች መካከል በመንግሥትና በሕዝባዊ አገልግሎት ግንኙነቶች መካከል ከፍተኛ ችግር የሚፈጠረው በኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ምክንያት በመሆኑ ከሥሩ ነቅሎ ለመጣል ያለርህራሄ መሥራት ያስፈልጋል።

4. ቃልን መጠበቅ

የሀገራችንን ባህል/ልማድ ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብን «የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ» የምንል ሕዝቦች ነን። ቃል አባይ መሆን በባህላችን የተወገዘ ነው። በዚሁ ተቸክለን መኖር አብቅተን «የተናገሩት አይጥፋ የወለዱትም ይፋፋ» ወደሚል ከፍታ መሸጋገር አለብን። ቃላችንን መብላት የለብንም። አንድ ለመቁረጥ ሦስት ጊዜ መለካት ያስፈልጋል። እንኳንስ የመንግሥት ቃል የግለሰብም ቃል ይጠበቃል፤ ይከበራል። ሕፃናት ልጆች ሳይቀሩ ወላጆቻቸው የገቡላቸው ቃል እንዲጠበቅላቸው ይሻሉ። ፈጽሞ አይረሱም። ቃል አለመጠበቅ ሲዘወተር በተናጋሪው ላይ እምነትን ያሳጣል። ንቀትን ያመጣል። ወሬ ብቻ ወደሚያሰኝ አቋምም ያደርሳል። ቃላችንን እንጠብቅ ለሕዝባችን ማድረግ ያለብንን ሁሉ ሳይሆን ማድረግ የምንችለውን ብቻ ይዘን ወደ ሕዝብ እንቅረብ። ትናንሽ ጥያቄዎች እዚህም እዚያም በተነሱ ቁጥር የማይፈፀሙ ቃሎችን መግባት አያስፈልግም። ቃል መግባት የግድ ከሆነ በአቅማችን እንግባ በሂደት ሊፈጠሩ የሚችሉ እንቅፋቶችን አስቀድመን እንተንብይ። ተግባራዊ ለማድረግ ያለንን አቅምና ግብአት እንለይ። የሕይወትን ፊልም ልብ አንጠልጣይ ማድረግ ምናልባት ጊዜያዊ እፎይታ ያስገኝ እንደሆነ እንጂ ዘላቂ እርካታን አያመጣም። የማንችለውን ነገር ቃል ላለመግባት ቃል እንግባ። ካለፉት ተሞክሮዎች ልምድ እንቅስም። ቃል የገባናቸውን ጉዳዮች በየዘርፉ በሥራ ዕድል ፈጠራ በመኖሪያ ቤት ግንባታ... ወዘተ እያልን እንቁጠር። ከነዚህ ውስጥ ምን ያህሉን ተግባራዊ እንዳደረግን እንስፈር። በምን ያህል ጊዜ፤ በምን ያህል ጥራት በምን ያህል ውጤታማነት እያልን እንለይ። ቃላችንን ላለመጠበቅ እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን እናጥራ። ለሚቀጥለው ምን ያህል ቃል እንደምንገባ እንገምት። ቃላችንን ለመጠበቅ እንሥራ!

 

ግርማ ለማ

Published in አጀንዳ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።