Items filtered by date: Tuesday, 03 October 2017

 

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አህጉር አቀፍ ውድድር ለማዘጋጀት በተቃረበበት ወቅት ዘወትር ፈተና ይገጥመዋል። እ..አ በጥር 2018 የሚካሄደው የዘንድሮው የአፍሪካ አገራት ቻምፒዮን ሺፕ (ቻን) ውድድሩም ከመሰል ዕጣ አላመለጠም።

የውድድሩ አዘጋጅነት ኃላፊነት የተሰጣት ኬንያ የመስተንግዶው ነገር አልሆን ብሏታል። ውድድሩን ለማስተናገድ የሚያስፈጉ ስታዲየሞች መሰረት ልማት ግንባታዎችን በታቀደላቸው የጊዜ ገደብ ማገባደድ አልቻለችም። ውድድሩን በናይሮቢ፣ ማቻኮስና ሞምባሳ በሚገኙ አምስት ስታዲየሞች ለማስተናገድ አቅዳ የነበረ ሲሆን፣ ከአምስቱ ስታዲየሞች የተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ብቻ ናቸው።

ከዚህ ባሻገር ከወር በፊት የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአገሪቱ በቅርብ የተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በስልጣን ላይ ያሉት ኡሁሩ ኬንያታ ተቀናቃኛቸውን ራይላ ኦዲንጋን በልጠው አሸንፈዋል ያለውን የኬንያ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሽሬ ዳግም አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ውሳኔ አሳልፏል።ይህን ተከትሎም የአገሪቱ መንግሥት ፊቱን ወደ ምርጫው አዙሯል። ሙሉ ትኩረቱን ወደ ምርጫ በማድረጉም ለቻን ውድድር መስተንግዶ ትኩረት ነፍጎታል።

ይህን ከግምት በማስገባት አገሪቱ ውድድሩን ለማስተናገድ ያልተሳካ ጥረት ማድረጓን በመገምገም የካፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጋና ርዕሰ መዲና አክራ ከሳምንት በፊት ባደረገው ስብሰባ የምስራቅ አፍሪካዋ አገር ውድድሩን እንዳታዘጋጅ ወስኗል፡፡

ካፍም ከኬንያ የነጠቀውን የቻን አዘጋጅነት መብት ለሌላ አገር በቀናት ውስጥ እንደሚሰጥ ይጠበቃል። ይሁንና የቻን ውድድር እንደ አፍሪካ ዋንጫ ብዙ እውቅናና ዝና የተጎናፀፈ አይደለምና አገራት ውድድሩን ለማዘጋጀች ብቻ የሚሳተፉበት የቻን ዋንጫ እስካሁን ማረፊያው አልታወቀም።

በጉዳዩ ላይ ሃሳባቸውን የሚያስተላልፉ የመገናኛ ብዙሃን ሐተታ እንደሚያመላክተውም፤ ተቋሙ በኬንያ ምትክ ውድድሩን እንዲያዘጋጅ የመረጠው አገር በይፋ ባይታወቅም ከሞሮኮ፣ ዛምቢያና ደቡብ አፍሪካ አንዱ የማስተናገድ መብት ሊሰጠው ይችላል።

በተለይ ሞሮኮ ያመለጣትን የ2015 አፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነት በቻን ለማካካስ ፍላጎት አሳይታለች። ውድድሩን ለማስተናገድ የሚያስችል በቂ መሰረተ ልማትን የማዘጋጀት አቅም ስላላት ከሌሎች አገራት የተሻለ ዕድሉን ልታገኝ ትችላለች የሚለው ግምትም ወደ ሞሮኮ አጋድሏል።

ኢትዮጵያም ይህን መድረክ የማዘጋጀት ፍላጎት ካላቸው አገራት ግንባር ቀደም ናት።ይህን ፍላጎቷንም ቀደም ባሉት ዓመታት ደጋግማ ስትገልፅ ቆይታለች። አፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ያላትን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን አቅምም እንደሆነ ለማሳየት፤ ይህን ውድድር አዘጋጅታ ማስመስክር ትፈልጋለች።

ታላላቅ ስፖርታዊ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም እንዳላት ካፍን ለማሳመንም ይህን የቻን ውድድር እንደ ማሟሻ የመጠቀም ፍላጎት አላት። ለዚህም ቀደም ሲል የ2020 የቻን ዋንጫን ለማዘጋጀት ጥያቄ ማንሳቷ ይታወሳል። ትናንት ከካፍ በወጡ መረጃዎችም ኢትዮጵያ ከኬንያ የተነጠቀውን የማዘጋጀት መብት መጠየቋ ተሰምቷል። ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ውድድሩን የማዘጋጀት ወርቃማ ዕድል ሊገጥማት እንደሚችል አሳማኝ ምክንያቶች እየቀረቡ ይገኛሉ።

ኬንያ ውድድሩን የማዘጋጀት ዕድል ያገኘችው ካፍ ዋናውን የአፍሪካ ዋንጫም ይሁን የቻንን ውድድር አዘጋጅነት በተደጋጋሚ ለምስራቅ አፍሪካ ዞን ባለመስጠቱ የተነሳ ነው። የአፍሪካ ዋንጫን ብንመለከት እንኳን ቀጣዮቹ ሦስት የአፍሪካ ዋንጫዎች ለምዕራብ አፍሪካ አገራት ነው የተሰጡት። ስለዚህም አህጉራዊ ውድድሮችን የማዘጋጀት ዕድል ፍትሃዊ ይሆን ዘንድ ቢያንስ የቻን ውድድር ለኬንያ መሰጠቱ ታምኖበት ነበር። አሁን ግን ይህ ዕድል ዳግም ከምስራቅ አፍሪካ ተነጥቋል። ነገር ግን ይህን ዕድል ከምስራቅ አፍሪካ ላለማራቅ ካፍ ኢትዮጵያን እንደ አማራጭ ሊወስድ ይችላል። እናም ይህም ውድድሩን ለማዘጋጀት ከቋመጡት ደቡብ አፍሪካና ሞሮኮ የመሳሰሉ አገራት ይልቅ ኢትዮጵያ የተሻለ ዕድል ሊያሰጣት ይችላል።

መድረኩን ማስተናገድ ግን እንዲሁ በፍላጎት ብቻ የሚሆን አይደለም።ለማዘጋጀት የሚያስችል አቅምን ማሳየትና ማስመሰከር የግድ ይላል። በርካታ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታዎችን መገንባትን ይጠይቃል። የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነት ዕድልን የሚወስነው ካፍ ላለፉት ጊዜያት ፊቱን ወደ ምስራቅ አፍሪካ ሳያዞር የቆየበት ዋነኛው ምክንያትም አገራቱ ከድህነት በታች ከመገኘታቸው ባለፈ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ባለቤት ባለመሆናቸውም ጭምር ነው።

እናም ለስፖርት መሰረተ ልማት በተለይ ለስታዲየም ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ተግባራት በማከናወን ላይ ትገኛለች። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መመልከት እንደተቻለው በከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በመላ አገሪቱ በተለያዩ ክልሎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ግዙፍ ስታዲየሞች እየተገነቡ ናቸው።

አገሪቱ በያዘችው ሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከ13 በላይ አዳዲስ ስታዲየሞችን በግንባታ ላይ መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።አገሪቱም የአህጉሩን ታላቅ የእግር ኳስ ውድድር ለማዘጋጀት ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ በመመደብ ውድድሩን ከሚያዘጋጁ ጥቂት አገራት ለመሰለፍ አዳዲስ የስታዲየም ግንባታዎችን በመላው ሀገር እያከናወነች ትገኛለች፡፡

የካፍ ፕሬዚዳንት ማዳጋስካራዊው አህመድ አህመድ የካፍ ፕሬዚዳንት ሆነው ወደ ተመረ ጡበት ምድር ኢትዮጵያ ከሰሞኑ ብቅ በማለት የአገሪቱ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ የካፍ አካዳሚንና በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለው የብሔራዊ ስታዲየም የግንባታ ሂደት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

አገሪቱ በስፖርት መሰረተ ልማት በተለይ ለእግር ኳሱ ዕድገት ከፍተኛ ወጪ በመመደብ እያከናወነች የምትገኛቸውን የተለያዩ ተግባራት አድንቀዋል። አገሪቱ በተለይ ለእግር ኳስ ልማት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የምታከናውናቸው መሰል ተግባራትም ለስፖርቱ ዕድገት ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው ሳያመላክቱም አላለፉም። አሁን ላይ በኢትዮጵያ እየተመለከቱ ያለው ተግባራት አገሪቱ አህጉራዊ ውድድሮች ለማዘጋጀት ዝግጁ መሆኗን ፍላጎቷንም በስኬት የማድመቅ ተስፋ እንዳላት መናገራቸው ይታወሳል።

መላ አገሪቱ ከስታዲየም ግንባታ በተጓዳኝ ለእንግዶች መስተንግዶ ግልጋሎት የሚሰጡ ግንባታዎች ተጧጡፈዋል። በእነዚህ ከተሞች በተለይም ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። ከተሞቹ የቱሪስት መዳረሻ እንደመሆናቸው በአገልግሎት አሰጣጥ በርካታ አገር ጎብኚዎች ማስደስት ችለዋል።የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን በማስተናገድም አቅማቸውን አሳይተዋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉትም፤በግንባታ ምዕራፍ ላይ የሚገኙትም ቢሆን ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም።ይህ የከተሞች ዕድገትና የስታድየሞች ግንባታ መፋጠን እንዲሁም የመሰረተ ልማት መስፋፋት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ ዕድሏን ያሰፋዋል።

መሰል የስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታዎች መስፋፋት ደግሞ ትላልቅ አህጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው ውድድሮች በአገሪቷ እንዲዘጋጁ የዕድል በር ይከፍታል። የቻን ውድድርን ለማዘጋጀትም ተመራጭ ሊያደርጓት እንደሚችል ታምኗል።አገሪቱ ታላላቅ ስፖርታዊ መድረኮችን የማስተናገድ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን አቅም እንዳላት ምስክርነት ይሰጣል።እዚህ ላይ የተቋሙ ፕሬዚዳንት እማኝነት ሲታከል ደግሞ ኢትዮጵያ ውድድሩን የማዘጋጀት ዕድሏ እንደሚሰፋ ድጋፍ ይሆናል።

በአሁኑ ወቅት አንጎላ፤ቡርኪናፋሶ፤ካሜሩን፤ ኮንጎ፤ ኢኳቶሪያል ጊኒ፤ኮትዲቯር፤ ሊቢያ፤ ሞሪታኒያ፤ ሞሮኮ፤ናሚቢያ፤ ናይጄሪያ፤ ሱዳን፤ ኡጋንዳና ዛምቢያ በዚህ ውድድር ለመካፈል ማጣሪያውን አልፈው ውድድሩን በጉጉት እየጠበቁ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም ዕድሉን ከቀናት በኋላ ተቀብላ ውድድሩን ለማዘጋጀት በመንደርደር ላይ ትገኛለች። የኬንያ መነጠቅና አገራት ውድድሩን ለማሰናዳት ዳተኛ መሆናችን ግን ለኢትዮጵያ ወርቃማ ዕድል እንደሆነ ብዙዎች ተስማም ተውበታል።

 

ታምራት ተስፋዬ

 

Published in ስፖርት

 

ሴቶች በተለያዩ ፈርጆች ላይ የሚኖራቸው ጠንካራ አቅም፣ አቋም፤ ዕውቀት፤ ተሞክሮ፤ የሃሳብ አፍላቂነትና ንቁ ተሳታፊነት ለማንኛውም ህብረተሰብም ሆነ አገር ውጤት፤ እድገትና ብልፅግና እጅግ ወሳኝ፤ ፋይዳውም ጉልህ ነው። የሴቶች መሰል አካላዊም ሆነ ዓዕምሯአዊ አስተዋጽኦና ስኬታማ ውጤት ጎልቶ ከሚስተዋልባቸው ፈርጆች መካከል ደግሞ ስፖርት ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይሰለፋል።

ስፖርት ፆታ አይለይም። በአንድ ፆታ ብቻ አይወሰንም፤ እድሎአዊም አይደለም። የስፖርት አመራርነትም ቢሆን እንደዚሁ ነው። ፆታን አይመርጥም። ይህ ሁሉ ግን ዕውነትነት የሚያገኘው ውድድርን መሰረት አድርገን ስንቃኘው ብቻ ነው። ሴቶች ከተሳትፎና ተወዳዳሪነት በዘለለ በስፖርት አመራርነት ሚና ያላቸውና የተሰጣቸውን ሚና ስንቃኝ አድሎአዊነትን በቀላሉ እንመለከታለን።

በጣት ከሚቆጠሩ አገራት በስተቀር በስፖርቱ አመራርነት ወንበር ለማጌጫ የቀረቡ በሚመስል ሁኔታ አንዳንድ ሴቶች ከመኖራቸው በስተቀር ይህ ነው የሚባል የእንስቶች ተሳትፏቸው በአግባቡ አለመስተዋሉ ደግሞ ለዚህ ምስክር ይሰጠናል።

ሴቶች በስፖርቱ በአምራርነት ይሳተፉ ከተባለውም የተቀመጠው ህግን ለማሟላት ብቻ እንጂ በአግባቡ ስልጣናቸውን እንዳይጠቀሙና በራሳቸው ውሳኔ እንዳይፀኑ ጫና እንደሚደረግ ባቸውም ሳይታለም የተፈታ ሃቅ ነው።

በመሰል ፆታዊ አድሎና የተንሸዋረረ እይታ ሰበብ ታዲያ ዛሬም ድረስ ሴቶች በስፖርቱ ዘርፍ በአመራር ሰጪነት አይታዩም። ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ይህ ችግር ተመሳሳይ መልክ ይይዛል። በአገሪቱ ከአጠቃላዩ ህብረተሰብ ከግማሽ በላይ ለሆኑት ሴቶች በስፖርት መስክ የተሰጣቸው ሚና አነስተኛ ሆኖ ይስተዋላል። የፌዴሬሽኖች ሥራ አስፈፃሚዎችን በመምረጥ በኩል አብዛኛው ትኩረት ለወንዶች ሲሰጥ ይታያል፡፡ ሴቶች ተወካዮች የሉንም። በአጠቃላይ ሴት ተወዳዳሪዎችን ከማፍራት በተጓዳኝ በስፖርት አመራርም ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት አልተቻለም።

ኢትዮጵያ በተለይ በሴት ስፖርተኞቿ በርካታ ስኬቶችን አግኝታለች፤ እያገኘችም ትገኛለች፡፡ የአገሪቱ እንስት ስፖርተኞች የውጤታማነት ጉዞም ከአገር ተሻግሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ጎልቶ የሚንፀባርቅ ነው። ይሁንና በአገሪቱ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ሴቶች በአመራርነት ያላቸው ተሳትፎ ገና ብዙ የሚቀሩት መሆኑ በቀላሉ ይታያል።

ሴቶች ወደ ስፖርት አመራርነት እንዲመጡ የምናስቀምጠው ልኬት ውፍረቱም ይሁን ቅጥነቱም፤ ጥልቀቱም ሆነ ስፋቱ አይታወቅም። እጅግ ከባድ እጥረት የሚታይበት የፆታ ተኮር የአመራርነት ተዋጽኦ ውስጥ ተደጋግሞ የሚነሳው ሴቶች ወደ ስፖርቱ አመራርነት እንዳይመጡ ያደረጋቸውን ተግዳሮቶች ምን እንደሆኑና እንዴት መሻገር እንደሚችል ለማሳየትም ይሰንፋል።

በዚህም ምክንያት አሁን አሁን የስፖርት አመራርነት ሃላፊነት ለወንዶች ብቻ የተፈቀደና የተተወ መስሏል። ሴቶችን ወደ ጥግ ወርውሯል። በወንዶች የበላይነት የተዋጠና ኢፍትሃዊነት የሚስተዋልበትም ሆኗል። የስፖርት አስተዳደሩ ምንግዜም በወንዶች ብቻ የሚተወን ነው። ማንኛውም በአገሪቱ የሚገኙ የስፖርት ፌዴሬሽኖችም ሆኑ ማህበራት በጠቅላላ ጉባኤያቸውም ሆነ በወቅታዊ መግለጫቸው አንድም ሴት ወክለው በመድረክ አለመታየታቸውን መለስ ብለን ከቃኘን ደግሞ ይህን ለማለታቸው ጥሩ ማስረጃ ይሆነናል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ምንም እንኳን በስፖርት ውድድሮች የሴቶች ተሳትፎ 45 በመቶ ቢደርስም በአመራርነት ድርሻ ግን ገና እጅግ አነስተኛ ነው። በአገሪቱ አጠቃላይ የስፖርት መስክ በሚሠሩ ማህበራትና ፌዴሬሽኖች ውስጥ ካሉት ከ173 በላይ የሚሆኑ አመራሮች ውስጥ የሴቶች ድርሻ ከአስር አይበልጥም።

ቀደም ባሉት ዓመታት በስፖርቱ ልማታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የሴቶችን እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸው የማይካድ ነው። ይሁን እንጅ ችግሮቹ ለረዥም ጊዜ ሲጠራቀሙ የቆዩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ዛሬም ድረስ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ተመዝግቧል ለማለት አያስደፍርም።

ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በስፖርት ፌዴሬሽኖችና ማህበሮች የሚሠሩ አካላት ውሳኔ ሰጪ የሥልጣን እርከን ላይ ሴቶች በዝተው እንዲታዩ ጥረት ያደርጋል፡፡ ዓለም አቀፉ ኮሚቴ‹‹ቢያንስ 20 በመቶ ሴቶች መሆን አለባቸው›› ቢልም የኢትዮጵያ የሴት አመራሮች ተሳትፎ ግን ገና አምስት በመቶ እንኳን መድረስ አልቻለም፡፡

በስፖርት ውስጥ ያለው የሴቶች የአስተዳዳሪነት ተሳትፎ በየጊዜው ለውጥ ቢኖረውም ለውጡ እጅግ አዝጋሚ ነው። አዝጋሚ በኦሎምፒክ ኮሚቴም ሆነ በቦርድ አመራርነት የተቀመጡ እንስቶቻችን ቁጥር አሉ ከሚባል ይልቅ የሉም ለመባል በእጅጉ የሚቀርብ ነው።

የስፖርቱ አስተዳደር በአብዛኛው በወንዶች ጫንቃ ላይ የወደቀ ነው። ሴቶች በበርካታ ፌዴሬሽኖች የፆታ በደል ይደረግባቸዋል። ይገለላሉ። በቦርድም ሆነ በኮሚቴ በርካታ ሴቶችን አንመለከትም። ሴት የስፖርት ተቋማት ሥራ አስፈፃሚዎችም የሉንም። የሴት አሰልጣኞችም ሆነ የቡድን መሪዎች ቁጥር አሁንም በሚገባው ደረጃ አላደገም። በዳኝነቱም ቢሆን ቁጥራቸው እጅግ ዝቅተኛ ነው።

በአገራችን ያሉት የስፖርት ተቋማት ሴቶች ወደ አመራር ስጪነት ለማምጣት አሊያም ከማብቃት የሚያስችል ፕሮግራሞች እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል። ይሁንና በተጨባጭ ግን ምንም ሲሠሩ አይስተዋልም። ያለመሥራታቸው ምስክር ደግሞ ከላይ የጠቀስናቸው ምክንያቶች በቂ ምስክር ይሆናል። ይሄ የሆነው ግን ሴቶች መሥራት ሳይችሉ ቀርተው አይደለም። የአመለካከት ችግር ውጤት ነው። በዚህ ረገድ ያለውን ትልቅ ድክመት በዘላቂነት ለመፍታትም ቀጣይ ሥራዎች በአግባቡ እየተፈተሹ መከናወን ይገባቸዋል፡፡

እናም ይህን ችግር ለማስወገድ ሴቶችን እንዴት ወደ ስፖርት አመራርነት ማምጣት ይቻላል የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው። ለዚህ ጥያቄ የመጀመሪያው ማጠንጠኛ ሴቶች ራሳቸውን በስፖርቱ አስተዳደርና አመራርነት ውስጥ ለማሳተፍ ያላቸው ጥልቅ ፍላጎት ላይ ይንተራሳል። ሴቶቹ የተሳታፊነት ፍላጎት ቢኖራቸውም ግን ይህ ብቻውን በቂ አይደለም። ብዙም ርቀት አያስኬድም።

የሴቶች ፈቃድ ለመተግበር ምቹ መደላድል የሚፈጥሩና በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ነባራዊ አምዶች የተመቻቹ መሆን ይኖርባቸዋል። ሁኔታዎቹን መልካም የሚያደርጋቸውም ደግሞ መልካም ሊባል የሚችል የምርጫ ሥርዓት ዕውን ሲሆን ነው። ሴቶቻችን በአንድ አገር ውስጥ ለሚኖራቸው የሁለንተናዊ የአመራር ሰጪነት ተሳትፎ አገሪቱ ውስጥ ባሉት እነዚህ ጭብጦች ላይ ይወሰናል።

ከዚህ በተጓዳኝ ሴቶቻችን በራሳቸው የመተማመን አቅምን ማጎልበት ይገባቸዋል። ፆታ ተኮር ንቅናቄ መፍጠርም አግባብ ይሆናል። ከፆታዊ የተንሸዋረረ እይታ የነፃ ማህበረሰብ መኖር ለሴቶች ወደ ስፖርት አምራርነት መቅረብ የሚኖረው ፋይዳ ነጋሪ አያሻውም። ለሴቶች ተወካይነት መጎልበት ፋይዳው ጉልህ ነው። ስፖርትን መምራት ለሴቶች እንግዳ ሁኖት አይደለም ብሎ የሚያምን ማህበረሰብ እንስቶችን ወደ አመራርነቱ ለማምጣትም ሆነ ያሉትን ለማጎልበት አይቸገርም። እናም የስፖርት አመራርነት ሚናና ድርሻው በወንዶች ብቻ ያልታጠረና የማይበየን መሆኑን የሚያምን ማህበረሰብ መፍጠርም ይኖርብናል። በዚህ እሳቤ በታጠረ ማህበረስብ ውስጥ የእንስቶች ወደ ስፖርት አመራርነት ሚና መቅረብ የማይታሰብ ነው።

ሴቶች ከተሳትፎና ተወዳዳሪነት በዘለለ ወደ አመራሩ መምጣት ብቻ ሳይሆን መብዛት ይኖርባቸዋል። የሴቶችን ወደ ጎን መግፋት መግታት የሚቻለው እነርሱን ወደ ስፖርት አመራርነቱ ስናመጣ ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ድምፅን ወደ ወንበር ቁጥር ለመቀየር የሚያስችል ተመጣጣኝ የውክልና ሥርዓት መቀየስ ይኖርብናል። ይህም ለሴቶች የተሻለ አውድ ይፈጥርላቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ሴቶች በስፖርት አስተዳደር ያላቸውን የአመራርነት ሚና ለማሳደግ ወደ አመራርነቱ እንዳይመጡ መሰናክል የሚሆኑ ማነቆዎችን ማስወገድም ለነገ የሚቀመጥ የቤት ሥራ መሆን የለበትም። በቦርድም ሆነ በኮሚቴ በርካታ ሴቶችን መመልከት ይኖርብናል። ለመሳተፍ ፈቃደኛ የሆኑ ሴቶች ደግሞ ራሳቸውን በአመራርነት ለማውጣት መትጋት ይኖርባቸዋል።

ስፖርትን መምራት ለሴቶች እንግዳ ሆኖ አይደለም። በአንዳንድ አገራት ሴቶች በስፖርቱ አመራርነት ያሳትፋሉ። የሴቶች የስፖርት አመራር በተለይ ለሴቶች ስፖርት እድገት ጉልህ ፋይዳ አለው። እናም የእንስት መሪዎች ቁጥር ማደግ በርካታ ጥቅሞች አሉት። በመሆኑም ብዙ የመሥራት አስፈላጊነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይሆንም፡፡ ወደ ስፖርቱ አመራርነት የሚመጡ ሴቶች ወደ ዘርፉ ለመቅረብ የሚያስችላቸው አማራጮችን ማሰብ ይገባናል እንላለን።

 

ታምራት ተስፋዬ

 

 

Published in ስፖርት

አንዳንድ ጊዜ ስሜታችንን አልያም ፍላጎታችንን አስቀድመን የሚያስከትለውን መዘዝ ሳናስብ እንጓዛለን ። ይህ ሁኔታ ደግሞ ያልታሰበ ችግር ውስጥ ከመክተቱም በላይ እናገኘዋለን ብለን ካሰብነው ጥቅም አልያም ደስታ እጥፍ የሆነ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል። በርካቶችም በተመሳሳይ ሁኔታ ቀልባቸው ያዘዛቸውን ነገር ብቻ በመፈፀም የማይወጡት ችግር ወስጥ ገብተዋል። እንደውም ችግራቸው ለሌሎችም ተርፏል።

ለዚህ አባባሌ መነሻ የሆነኝ ደግሞ ኦዲቲ ሴንትራል አንድን ነገር ከማድረጋችሁ በፊት ሁለት ጊዜ ማሰብ ያስፈልጋል በማለት ከወደ ካናዳ ኦሀዩ ግዛት ያሰማን ዜና ነው፤ ካት ጋልነር የ24 ዓመት ወጣት ናት። የወጣትነት ቅብጥብጥ ፍላጎቷ አስገድዷት ነው መሰል የአይኗን የውስጠኛ ክፍል በሀምራዊ ቀለም ለመነቀስ ትወስንና ታደርገዋለች፤ ምንም እንኳን ውጤቱ እርሷ እንዳሰበችው አስደሳች ባይሆንም።

አጌጥበታለሁ ለየት ብዬም እታይበታለሁ በማለት በርካታ ዶላሮችን ያፈሰሰችለት ንቅሳት ግን እንዳሰበችው ውጤታማ ከመሆን ይልቅ ዓይኗ ሀምራዊ እንባ እንዲያወጣ ብሎም እይታዋ የቀነሰ እንዲሆን አድርጓት ለአስቸጋሪ የጤና ሁኔታም ዳርጓታል።

የዓይኗን ጤንነት በመከታተል ላይ ያሉት ዶክተርም ስለ ወጣቷ ሲናገሩ « በቀጣይ የወጣቷ ዓይን ምናልባትም ለረጅም ዓመታት ጥርት ያለ እይታን ላያሳያት ይችላል። ምናልባት ችግሩ ሊቀረፍ የሚችለው ዓይኗ ላይ ቀዶ ህክምና ቢደረግላት ነው » በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ጋልነርም በማህበራዊ ድረ ገጿ ላይ ለወዳጆቿ እንዳለችው « ሰዎች እባካችሁ አንዳንድ ጊዜ ስሜታችሁን አትከተሉ እኔ ይህንን በማድረጌ የማልወጣው ጣጣ ውስጥ ገብቻለሁ እናም ምንም ነገር ለማድረግ ስታስቡ ሁለት ሦስት ጊዜ አስቡ» ማለቷን ዘገባው አስነብቧል።

 

እፀገነት አክሊሉ

 

 

Published in መዝናኛ
Tuesday, 03 October 2017 18:23

ጥንቸልን ለረሃብ ማስታገሻ

ረሃብን ለማስታገስ የሚውሉ በርካታ የም ግብ አይነቶች ቢኖ ሩም እንደየ አገራት ባህልና ዕምነት ከቦታ ከቦታ ይለያያሉ፡፡ በአገራችን ለምግብነት ከሚውሉ እንስሳት ውስጥ ብዙ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ በዓለም ላይ የሚገኙ አገራት ከጥቃ ቅን ነፍሳት ጀምሮ እስከ ትላልቅ አውሬ ዎች የሚመገቡ ከመኖ ራቸው አኳያ በአገራ ችን ለምግብነት የሚ ውሉ እንስሳት ውስን ናቸው ማለት ይቻ ላል፡፡ ይህም ባህላች ንና ዕምነታችን እነዚ ህን ፍጥረታት ለመ መገብ ስለሚከለክል ነው፡፡

ከወደ ደቡብ አሜሪካ ከሰሞኑ የተሰማው ዜና ግን ቬንዙዌላ የተሰኘችው አገር የዜጎቿን የምግብ ፍላጎት ለማርካትና ረሃባቸውን ለማስታገስ ጥንቸሎችን አርብቶ ገፎና በልቶ ማጣጣም ሁነኛ መፍትሄ ነው ትላለች፡፡

ሮይተርስ ከቬንዙዌላ ርዕሰ ከተማ ካራካስ እንደዘገበው መንግሥት በዚህ ሳምንት አንድ ቀጭን ትእዛዝ እንዳስተላለፈ ይነግረናል፡፡ ይኸውም በአገሪቱ የምግብ እጥረት መከሰቱን ተከትሎ ዜጎች ጥንቸሎችን በቤታቸው በማርባት ለምግብነት እንዲያውሏቸው ነው፡፡

ይህ ‹‹የጥንቸል ፕላን›› የተሰኘው እቅድ በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ የምግብ አቅርቦትን ከፍ ለማድረግ የተወጠነ እንደሆነ ነው ዘገባው የሚያስረዳው፡፡

‹‹የባህል ችግር እንዳለ ይገባናል ምክንያቱም ጥንቸሎች የሚያምሩ የቤት እንስሳት ናቸው፡፡›› ሲሉ ነበር የአገሪቷ የግብርና ሚኒስቴር ፍሬዲ በርናል በቴሌቪዥን ስርጭት ከፕሬዚዳንት ማዱሮ ጋር በመሆን በዚህ ሳምንት የተናገሩት፡፡

እንደሳቸው ገለፃ ጥን ቸል ቆንጆ እንስሳ ሳትሆን 2.5 ኪሎ ወይም 5 ነጥብ 5 ፓውንድ በሚመዝን ፕሮቲን የበለፀገና ምንም አይነት ኮሌስት ሮል የሌለበት ሥጋ እንዳላት በይፋ ተና ግረዋል፡፡

ዘገባው እንደሚያስ ረዳው የአገሪቱ ገዢና የሁለት ጊዜ የፕሬዚ ዳንታዊ ተመራጩ ተቃዋሚ ሄነሪኬ ካፕ ሪል ‹‹ ዕውነት ነው? በርግጥም በአገ ራችን ሰዎች ጥንቸሎ ችን በማርባትና ለምግ ብነት በማዋል የረሃብ ችግራ ቸውን የሚቀርፉ ይመ ስልሃል? ›› ሲሉ በቪዲዮ ለግብርና ሚኒስትሩ በርናል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የጥንቸል የምግብ ፍጆታ በተለይም በአውሮፓ ከፍተኛ ቢሆንም በአሜሪካ ግን ዝቀተኛ መሆኑ ይታ ወቃል፡፡ እንደ ተባበሩት መንግሥታት የምግብና ግብርና ድርጅት ከሆነ እነዚሁ ጥንቸሎች ከአሳማና ሌሎች ለምግብነት ከሚውሉ እንስሳቶች ሥጋቸው የተሻለ ፕሮቲን እንደያዘ ይገልፃል፡፡

ይሁን እንጂ በአሁኗ ቬንዙዌላ ጥንቸሎችን በብዛት ማርባት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችልና በተለይም አገሪቷ እያጋጠማት ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የጥንቸል ኢንዱስትሪውን ለመገንባት ከሚጠይቀው ወጪ አንፃር ከባድ ፈተና ሊገጥማት እንደሚችልም ነው ዘገባው የገለፀው፡፡

 

አስናቀ ፀጋዬ

Published in መዝናኛ

 

አትመም አይባልም ፣ ማር ነው እንጂ ይላሉ አበው፡፡ አዳዲስ በሽታዎች ሲከሰቱ እና ህክምናውም የሚረዳው በሌለ ጊዜ እንዲሁም አንዳንድ የቆዩ በሽታዎች በህክምናው ዘርፍ ዘላቂ መፍትሄ ሳይኖራቸው ሲቀር ህሙማን አልፎም ተርፎ አስታማሚዎችና ቤተሰቦች ክፉኛ ይፈተናሉ፡፡

ለሞት መዳረግ፤ የአልጋ ቁራኛ መሆን፣ ተስፋ ቆርጦ ሞትን እየጠበቁ መኖር ይከተላል፡፡ በዚህ ሂደት የሚጎዱት ሕሙማን ብቻ አይደሉም፡፡ ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ጎረቤት፣ ወዘተ ጭምር ናቸው፡፡

እነዚህ ዜጎች የችግሩ ገፈት ቀማሽ ይሁኑ እንጂ ሀገርም መፈተኗ አይቀርም ፡፡ ይህ ችግር የህሙማኑን እና የቤተሰቦቻቸውን ጥሪት እያሟጠጠ እና ከምርት ሥራም ውጪ እያደረገ ይታከሙበት፣ ይመገቡት፣ ይጠለሉበት ሲያሳጣም ይስተዋላል፡፡

ይህ ችግር የህሙማኑን እና የቤተሰቦቻቸውን ጥሪት እያሟጠጠ እና ከምርት ሥራም ውጪ እያደረገ ይታከሙበት፣ ይመገቡት፣ ይጠለሉበት ሲያሳጣም ይስተዋላል፡፡ እነዚህ ዜጎች የችግሩ ገፈት ቀማሽ ይሁኑ እንጂ ሀገርም መፈተኗ አይቀርም ፡፡

ችግሮቹ ታዲያ ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይረዳም እንዲሉ የበሽታዎቹ ሰለባ ሕሙማን እና ቤተሰቦች በጋራ ወይም በማህበር ወደ መፋለም እንዲገቡ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ዛሬ በዚህ አይነት መንገድ የካንሰርን ፣ የስኳርን፣ የኩላሊትን፣የኤች አይቪ ኤድስን ደዌዎች፣ ወዘተ. በማህበር የሚፋለሙ ጥቂት አይደሉም ፡፡

ማህበራቱ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር እንዲሉ ህሙማኑንና ቤተሰቦቻቸውን ከመታደግ ባለፈ በመንግሥት በኩል ከአቅምና ከመሳሰሉት ችግሮች በመነጨ ብዙም ትኩረት ሳይሰጣቸው የቆዩ በሽታዎች ትኩረት እንዲያገኙ እያደረጉ ናቸው፡፡

እነዚህ ማህበራት እየተበራከቱ መጥተዋል። አንዳንዶቹ በሚያገኙት የውጭ አገር እርዳታ የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ ከአባሎቻቸው በሚሰበስቡት ገንዘብ በሽታውን በአግባቡ መታከም ላልቻሉና የአቅም ወስንነት ላለባቸው ሰዎች የተለያዩ የህክምና እንዲሁም የምግብና የመጠለያ ድጋፎችን እያደረጉ ይገኛሉ።

ከማህበራቱ መካከል በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በካንሰር በሽታ ምክንያት አልጋ ይዘው በተኙና ህመምተኞቹን በሚረዱ የህክምና ባለሙያዎች አማካይነት በ1995 .ም የተመሰረተውና በአገሪቱ የመጀመሪያው የሆነው የኢትዮጵያ ካንሰር አሶስየሽን ይገኝበታል፡፡

ማህበሩ ከተመሰረተ አንስቶ የበርካታ ወገኖች ተስፋ እንዲለመልም እያደረገ ነው። ከግለሰብ በ20ሺ ብር በተከራየው ቤት 15 አልጋዎችን በማዘጋጀት በበጎ ፈቃደኞችና ተቀጣሪ የጤና ባለሙያዎች አማካይነት ህሙማኑን ይንከባከባል።

የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ በለጠ እንደሚናገሩት፤ ሁሉም የአቅሙን ቢያደርግ ችግሮችን ሙሉ በሙሉ መፍታት ባይቻል እንኳ ባሉበት በማቆም የህሙማኑን ተስፋ ማለምለም ይቻላል። ማህበሩም በዚህ መንፈስ የተቋቋመ እንደመሆኑ በችግሩ ውስጥ ለሚገኙ ሁሉ ተስፋ እየሆነ ነው፡፡

የካንሰር በሽታ ከባድ ህክምናውም ብዙ ወጪን የሚጠይቅና ልዩ ክትትልን የሚፈልግ ነው፡፡ በአገሪቱ ህክምናው የሚሰጠው በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ መሆኑም ችግሩን ውስብስብ በማድረግ በርካታ ህሙማን ተስፋ እየቆረጡና ህክምናቸውንም እያቋረጡ ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ለሞት ተዳርገዋል።

ማህበሩ በአነስተኛ ቤት ውስጥ በተለይም ከተለያዩ ክልሎች ወደ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመምጣት የህክምና አገልግሎት የሚከታተሉ እና ምንም ዓይነት ማረፊያ የሌላቸው ችግረኛ ሴቶች ሕክምናውን እስከሚጨርሱ ድረስ የምግብ፣ የመጠለያና የትራንስፖርት አገልግሎት በማመቻቸት እንክብካቤ ይደረግላቸዋል።

ከአዲስ አበባ ውጪ የሚኖሩ፣ የአቅም ማነስ እንዳለባቸው የሚገልጽና በሚመለከተው አካል የተረጋገጠ ደብዳቤም የሚያቀርቡ ሴቶች ይህ አገልግሎት እንደሚሰጣቸው አቶ ሀብታሙ ይገልጻሉ።

ማህበሩ እስከ አሁን ለ520 ችግረኛ ሴቶች የህክምና፣ የምገባና ንጽህና አጠባበቅን የተመለከቱ ትምህርቶች መስጠቱን፣ በህክምናው ምክንያት የሚሰሟቸውን የጎንዮሽ ችግሮች በመከታተል ሥራዎች መከናወናቸ ውንም ያብራራሉ።

እንደ አቶ ሀብታሙ ገለጻ፤ ማህበሩ ለሚያከና ውነው ተግባር የገቢ ምንጩ በዋናነት አባላቱ ሲሆኑ፣ ሌሎች በህክምና ሥራው ላይ የተሰማሩ እንዲሁም ይህን በጎ ተግባር የሚያከብሩ አካላትም እገዛ ያደርጋሉ።

ማህበሩ በዋናነት ሊሰራ የተነሳው ይህን ተግባር እንዳልሆነ አቶ ሀብታሙ ጠቅሰው፣ ህብረተሰቡ እርግማን ነው ብሎ የሚያስበውን የካንሰር በሽታ እርግማን አለመሆኑን ለማስገንዘብና የቅድመ ጥንቃቄ ትምህርት በተለያዩ ተቋማት እየተንቀሳቀሰ ለመስጠት ተከስቶም ሲገኝ እንዴት ህክምናውን ማግኘት እንደሚቻል ለማመላከት መሆኑን ያብራራሉ።

ይሁንና ማህበሩ ከሦስት ዓመት ተኩል ወዲህ በህብረተሰቡ ዘንድ ይህን ግንዛቤ ከመፍጠርና በቶሎ ወደ ህክምና ሂዱ ከማለት ባሻገር የበሽታው ተጠቂዎች ያለባቸውን ተደራራቢ ችግር በመገንዘብ ሴቶችን መርዳት መጀመሩን ይገልጻሉ።

አቶ ሀብታሙ እንደሚሉት ፤ከሦስት ዓመት ወዲህ መንግሥትም ለዚህ ችግር ልዩ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በቀዳማዊ እመቤት ሮማን ተስፋዬ እና በጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ የሚመራ «ናሽናል ካውንስል ኮሚቴ» ተቋቁሟል። በሌላ በኩልም የጨረር ህክምና ( ሬዲዮ ቴራፒ) ማሽኖች በ6 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ሥራ ላይ እንዲውሉ ይደረጋል፡፡ የኬሞቴራፒ ህክምና በየጤና ጣቢያው ተጀምሯል፤ይህ በጣም ጥሩ እርምጃ ነው። ቀጥሎም ነርሶችን፣ ሬዲዮሎጂስቶችንና ሌሎች ባለሙያዎችንም ማሰልጠን ያስፈልጋል። እነዚህን ማድረግ ከተቻለ ህሙማኑን በተወሰነ መልኩም ቢሆን መታደግ የሚቻል ከመሆኑም በተጨማሪ በአዲስ አበባ በአንድ ሆስፒታል ላይ ብቻ ተወስኖ የቆየው የህክምና አገልግሎት እየተስፋፋ ይመጣል ።

ይህ ሥራ አበረታች መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሀብታሙ፣ መንግሥት ማህበሩ ራሱን የሚያስተዋ ውቀበትን መንገድ በተለይ የመገናኛ ብዙኃንን የአየር ሰዓት በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት የሚችልበትን ሁኔታ እንዲፈጥርም ይጠይቃሉ፡፡ የማህበሩ አቅም በቤት ኪራይ ሳቢያ እየተዳከመ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ችግር የሚፈታበት መንገድ በመንግሥት በኩል እንዲታሰብበት አስገንዝበዋል።

ከሰሜን ወሎ ለህክምና አዲስ አበባ የመጣችው ወይዘሮ አስረበብ አድማሴ የአቅም ችግር እንዳለባት አስመስክራ በማህበሩ የመጠለያና ሌሎች አስፈላጊ ወጪዎቿ ተሸፍነውላት እየታከመች ትገኛለች። በሽታው ከጀመራት ከሁለት ዓመታት በላይ ሆኗል። ከዓመት በፊት ጀምሮም ህከምና እያደረገች ናት። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ኬሞቴራፒ እየተከታተለች ሲሆን፣ መጠነኛ ለውጦችንም በመመልከት ላይ እንደምትገኝ ጠቁማለች። ማህበሩም በምግብ፣ በመጠለያ እንዲሁም ወደ ህክምና ተቋም ስትሄድም ትራንስፖርት በማቅረብ ከፍተኛ እገዛ እያደረገላት መሆኑን ትናገራለች።

ሌላው ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ እንዲሁም በኤች. አይ. /ኤድስ ምክንያት የተጎዱትን በመርዳት በኩል ሰፊ ሥራ እያከናወነ ያለው መቅድም ኢትዮጵያ የተባለው ማህበር ነው። ማህበሩ ኤች. አይ. ቪ በደማቸው ውስጥ ባለባቸውና ሌሎች ወጣቶች የዛሬ 23 ዓመት የተመሰረተ ሲሆን፣ በአገሪቱም የመጀመሪያው መሆኑ ይነገርለታል።

የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ ዘመነ እንደሚሉት ፤ ማህበሩ እንደ አንጋፋነቱ ከተመሰረተ አንስቶ በበሽታው የተያዙ አባላቱን ከተስፋ መቁረጥና የአልጋ ቁራኛ ከመሆን የሚታደጋቸውን የምክር አገልግሎት ከመስጠት ጀምሮ በተለይም በበሽታው ተጎድተው አልጋ የያዙትን ቤት ለቤት በመዘዋወር የመንከባከብ ሥራ ሰርቷል።

በተለይም ከመንግሥት ህጋዊ እውቅና ካገኘ በኋላ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እየቀረጸ ከድጋፍና እንክብካቤ ሥራው በተጓዳኝ ለህብረተሰቡ ትምህርት ሲሰጥና የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን በሰፊው ሲሰራ መቆየቱን አቶ መንግስቱ ያብራራሉ።

እንደ ግንባር ቀደምትነቱም በአገሪቱ የኤች. አይ. ቪ ካውንስልና የፌዴራል ኤች. አይ. /ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት (ሀብኮ) በተቋቋመበት ወቅት በተደረገው እንቅስቃሴ ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረጉንም ያስታውሳሉ። ‹‹ከሀፕኮ በተገኘ ግብዓትና ገንዘብ በርካታ ማህበራትን አደራጅተናል›› የሚሉት አቶ መንግስቱ፣ በዚህም የበሽታውን ስርጭት በመግታቱ በኩል ሰፊ ሚና መጫወቱን ያብራራሉ።

እንደ አቶ መንግስቱ ማብራሪያ፤ማህበሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ኮንፈረንሶችን በመካፈልና ልምዶችን ወደ አገሪቱ በማምጣት ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረጉን፣ በአፍሪካም ተመሳሳይ ኮንፈረሶችን በመካፈልና የተለያዩ መሰል ተቋማት ጋር በህብረት በመስራት በበሽታው ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ የማስፋት ሥራም አከናውኗል።

እንደ አቶ መንግስቱ ማብራሪያ፤ ማህበሩ የኢትዮጵያ መንግስት ፀረ-ኤች.አይ./ኤድስ መድኃኒትን ወደ አገር ውስጥ ከማስገባቱ በፊት መድኃኒቱን አስገብቶ ያከፋፍል ነበር፡፡ አሁንም በራሱ ክሊኒክ ለቫይረሱ ተጠቂዎች ክትትልና ህክምናን ያደርጋል። በዚህ ሥራውም ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ሆነ ከሌሎች መንግሥታዊ አካላት ጋር ሰፊ የሥራ ግንኙነት አለው ። በአሁኑ ወቅት የማህበሩ ስድስት ቅርንጫፎች በሙሉ አቅማቸው እየተንቀሳቀሱ ሲሆን፣ ከ177 በላይ የሙሉ ጊዜ ሠራተኞችም አሉት፤ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር ይሰራል ፡፡

የፀረ-ኤች. አይ. /ኤድስ መድኃኒት ወደ ሀገር ውስጥ በስፋት ከገባ በኋላ ሥራዎች እየተቀዛቀዙ የህብረተሰቡ አስተሳሰብም ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እየተቀየረ መጥቷል የሚሉት አቶ መንግስቱ፣ የቫይረሱ ስርጭት እያገረሸ ነው።ይህ ችግር አሁንም የሁሉንም አካላት ርብርብና የተቀናጀ ሥራን ይጠይቃል ብለዋል።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሪፎርምና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ረዳት ዳይሬክተር አቶ አሰፋ አይዴ እንደሚሉት፤ በሀገሪቱ በጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ በርካታ ማህበራት ይገኛሉ፡፡ ማህበራቱ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በቅርበት ይሰራሉ፤ ህክምናዎች ተደራሽ እንዲሆኑ የማድረግ እንቅስቃሴ በመንግሥት በኩል ትኩረት እንዲያገኝ በማስቻል የላቀ ሚና አላቸው።

እንደ አቶ አሰፋ ገለጻ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከእነዚህ ማህበራት ጋር መስራቱ እንደሚጠቅመው ይረዳል፤ በመሆኑም እንደ አንድ የህዝብ ክንፍ አድርጎ ይጠቀምባቸዋል።በተለያዩ የወይይት መድረኮች ላይም እንዲሳተፉና ችግሮችን ነቅሰው እንዲያወጡ በማድረግ ለችግሮቹ መፍትሔ የማፈላለግ ሥራም ያከናውናል።

በተለይም ልዩ ትኩረት የሚሹ እንደ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ያሉ ማህበራት የጋራ ፌዴሬሽን በማቋቋም የአቅምና ሌሎችን ጥያቄዎችን በራሳቸው በመመለስ በኩል አበረታች ለውጦች እየታዩ መሆናቸውን አቶ አሰፋ ይጠቅሳሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት በኩላሊት ህክምና ላይ የተለያዩ ለውጦች ታይተዋል የሚሉት አቶ አሰፋ፣ ከዚህ በፊት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተወስኖ የቆየውን የዲያሌሲስ ህክምና በጳውሎስ ሆስፒታልም እንዲስፋፋ በማድረግ ከዚያም አልፎ የኩላሊት ንቅለ ተከላን በመጀመር አበረታች ለውጦች መምጣታቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ይህንንም ሥራ በዋና ዋና የክልል ከተሞች ለማስፋት መታቀዱን ያብራራሉ።

በተመሳሳይ በአንድ የህክምና ማዕከል ተወስኖ የነበረውን የካንሰር ህክምናንም በማስፋት በተጨማሪ በአምስት ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ላይ እንዲሰጥ የማድረግ እንቅስቃሴም መጀመሩን ያመለክታሉ።

በአጠቃላይ ከማህበራቱ ጋር መስራቱ የህሙማንን መረጃ በጠራ ሁኔታ ለማወቅ ከማስቻሉም በላይ ችግሮቻቸውን በማዳመጥ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት በኩልም አበረታች ለውጥ እንዲመጣ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

 

እፀገነት አክሊሉ

 

 

Published in ማህበራዊ

   

አቶ አስቻለው ተክሌ ፤                                       መጋቢ ዘሪሁን ደጉ፤                                   ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፤

 

ብዝሃነት የሰላም ስጋት የሚሆነው በማንነቶች መካከል እኩልነት ከሌለ ነው፡፡ ሁሉም ህዝቦች ዕኩል የመልማት፣ የማደግና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ካጡም ችግር ሊፈጠር መተማመንም ሊጠፋ ይችላል፡፡ ይህ ዓይነት ሁኔታ እየተገነባ ባለው የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ ተቀባይነት የለውም፡፡

ኢትዮጵያ የህዝቦቿን ብዝሃነት በአግባቡ ማስተናገድ በመቻሏ አስተማማኝ ሰላም እንዲኖራት አስችሏታል፡፡ ግጭት በማይለየው የአፍሪካ ቀንድ የምትገኘው ይህች አገር የራሷን ሰላም በአስተማማኝ ከመጠበቅ አልፋ የአፍሪካ አገራትንና መላው ዓለምን በሰላም ጥበቃ ስራ በማገዝ ግንባር ቀደም ሆናለች፡፡ ይህ የሆነው ውስጣዊ ሰላሟን በአስተማማኝ መሰረት ላይ በመገንባቷ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም በመገንባቱም ፍትሃዊ፣ ፈጣንና፣ ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ አስችሏል፡፡ ሆኖም እየተገነባ ያለው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሂደት እንደመሆኑ በአፈጻጸም ጉድለት የሚፈጠሩ ችግሮች አልፎ አልፎ ማጋጠማቸው አይቀርም፡፡ በቅርቡ በአንዳንድ አካባቢዎች ከወሰን ጋር ተያይዞ የተከሰተው ግጭት አብነት ሊሆን ይችላል፡፡ በግጭቱ ሳቢያ የበርካታ ዜጎች ደም ሲፈስ፤ ዜጎች ለዓመታት ሲኖሩባቸው ከነበሩ አካባቢዎችም እንዲፈናቀሉ አስገድዷል፡፡ ሰሞኑን እየደረሰ ያለው ዓይነት ግጭት በተደጋጋሚ ሲከሰት ማየት እጅግ አሳዛኝና በአፋጣኝ መቆም ያለበት ክስተት መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሰሞኑን በሰጠው መግለጫም አጽንኦት ሰጥቶታል፡፡

በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ግጭት አፈታት የሰላም እሴቶች ግንባታ ጥናትና ንቃት ህገ-መንግሥት ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ተክሌ እንደሚሉት፤ መነሻ ምንጫቸው የተለያየ የሆኖ ግጭቶች ወይንም ደግሞ ብጥብጦች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ግጭቶችን ለማስቆም ወይንም ለመከላከል የሚቻለው የተለያዩ ሥርዓቶችን በመዘርጋት ነው፡፡

ከግጭት ጋር ተያይዞ ብዙ ያልተሰራበትና ክፍተት አለበት ብዬ ከማስበው አንድ ጉዳይ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ያለመዘርጋት ነው፡፡ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ከግጭትና ከብጥብጥ ጋር ተያይዞ ያሉ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ያተኩራል፡፡ በህብረተሰቡ ውስጥ ቅራኔን ሊፈጥሩ፣ ጥላቻን ሊያቀጣጥሉ የሚችሉና ወደ ሁከትና ብጥብጥ የሚዳርጉ ድርጊቶችን እያዩ መረጃ የማሰባሰብና የማጠናከር ሥራ ነው፡፡ የተገኙ መረጃዎችን መሰረት አድርጎም ግጭቶችን አስቀድሞ የመከላከል ሥርዓት እንዲዘረጋ የማድረግ ትግበራ ሲሆን፤ አሰራሩን መዘርጋት ያስፈልጋል ይላሉ አቶ አስቻለው፡፡

እንደ አገር ግጭት ከመከሰቱ በፊት መከላከል ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆኑን የሚያሳስቡት ዳይሬክተሩ፤ ከተከሰተ በኋላ ደግሞ የሚፈታበትን የአሰራር ሥርዓት ተከትሎ መስራት ተገቢ መሆኑን፣ ግጭቱ ከተፈታ በኋላም ተጋላጭ ወገኖችን ቀድሞ ወደ ነበሩበት ቦታ በመመለስ የሰላም እሴት ግንባታ ሥራዎች መሰራት እንደሚኖርበት ያመለክታሉ፡፡ ግጭቶችን ለማስቆም እነዚህ ጉዳዮች በተገቢው መንገድ መተግበር እንዳለበትም ይገልጻሉ፡፡

ግጭት በየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚከሰት ነው በየደረጃው ያሉ ወገኖችም የግጭቱ ተዋናይ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚጠቁሙት ዳይሬክተሩ፤ አመራሩ አስቀድሞ የመከላከል፣ ከተከሰተ በኋላም ፈጥኖ መፍታትና የሰላም እሴት ግንባታ ሥራዎችን ለመስራት የግጭት መከላከልና አፈታት ላይ የአመራር ጥበብ ሊኖር ይገባል የሚል አቋም አላቸው፡፡ ህብረተሰቡ ሰላማዊና የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖር ከተፈለገ አመራሮች በተለይ ግጭትን ከመፍታት፣ ከመከላከልና ሰላም ከመገንባት አኳያ የአመራርነት ጥበብ ማዳበር ይገባቸዋል፡፡

አንዳንድ አመራሮች ህብረተሰቡን እንደ ሽፋን በመጠቀም ህዝብን በህዝብ ላይ የሚያነሳሱ፣ ጥላቻን የሚቀሰቅሱ፣ የተለያየ ትንኮሳን የሚፈጥሩ በአንዱ ጉዳት እጠቀማለሁ ብለው የሚያስቡ እና የሚንቀሳቀሱ አመራሮች አሉ፡፡ እንደእነዚህ ዓይነት አመራሮችን ህብረተሰቡ ሊታገላቸውና ሊያጋልጣቸው ይገባል ነው አቶ አስቻለው የሚሉት፡፡

በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ ወደ ግጭት የሚያመሩ ነገሮች በሳይንሱ ተለይተዋል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በተለይም የተፈጥሮ ሀብት ውስንነት ሲኖር ከእርሱ ጋር ተያይዞ እኔ ልጠቀም ከሚል ፍላጎት ግጭቶች ሊከሰት እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዳይፈጠር ሁሉም ያለውን ሀብት በፍትሃዊ አግባብ የመጠቀም፣ የመካፈል፣ ባህል ሊኖር ይገባል ሲሉ አቶ አስቻለው ይመክራሉ፡፡

በተፈጥሮ ምክንያት አንዱ የሃብት ባለቤት ሊሆን ሲችል፤ በአንጻሩ ሌላው ባይኖረው እንኳን የመተሳሰብ፣ ተደጋግፎ የመኖር የቆየ ባህልና ልምድን ማጠናከር ከህብረተሰቡ እንደሚጠበቅ ይናገራሉ፡፡ ሁከትና ብጥብጥ ሲገጥም የመጨረሻው ደረጃ የሚሆነው ግጭት እንደመሆኑም ለግጭት የሚዳርጉ ሁኔታዎች ሲከሰቱ አስቀድሞ የመከላከል ሥራ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም ያክላሉ፡፡

አቶ አስቻለው እንደሚያስታውሱት፤ ቀደም ሲል በነበረው ተሞክሮ ስለግጭት ሲነሳ ይፈራ ነበር፡፡ በመንግሥት ደረጃም ሆነ የተለያዩ አመራሮች ስለጉዳዩ ማንሳት አይፈልጉም፡፡ አሁን ግን ይህ እየቀረ መጥቷል፡፡ በቀጣይም መንስኤውንና መፍትሄዎቹን በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ መገናኛ ብዙሃንም ሚዛኑን የጠበቀ መረጃ ለህዝብ የማስተላለፍ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ስለሚነሱት ጥያቄዎች ትክክለኛና ሚዛኑን የጠበቀ መረጃ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ትክክለኛ መረጃ ከተደበቀ ማህበራዊ ድረ ገጾች የተደበቀን ነገር አወጣን ለማለት በቅብብሎሽ ሃሰተኛ መረጃ ያስተላልፋሉ፡፡ ይህ በህብረተሰቡ ውስጥ የቆየውን ወንድማማችነት፣ መተሳሰብና መተዛዘን እንዲሁም ሰላማዊ ግንኙነትን ሊያጠለሽ ወይም ሊያቆረፍድ ይችላል፡፡

አንዳንድ ግለሰቦች ሆን ብለው በፈጠራ ወሬ ነገር በመቆስቆስ ህብረተሰቡን ወደ ግጭት የሚገፋፉበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ህብረተሰቡ ሆን ብለው አደናጋሪ መረጃዎችን በመልቀቅ ግጭቶችን ለማባባስ አልመው ከሚንቀሳቀሱ አካላት ሊጠነቀቅ ይገባል ነው አቶ አስቻለው የሚሉት፡፡ ህዝብ የተረጋጋ ኑሮ እንዳይኖር የሚፈልጉ አሉ፡፡ ከእነዚህ አካላትና የመገናኛ ብዙሃን የፈጠራ ወሬ መጠንቀቅ ይገባል፡፡

ህብረተሰቡ የተፈጠረውን ትክክለኛ ነገር እንዲያውቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ መስጠት አለባቸው። ይህን ማድረግ ከተቻለ በአገር ውስጥ ያሉ አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ውጭ ካሉ አካላት ጋር በቅብብሎሽ የሚያስተላልፏቸው መረጃዎች ይከሽፋሉ፣፡

አቶ አስቻለው እንደሚያብራሩት፤ አሁን ዓለም በአንድ መረብ የተገናኘበት ወቅት እንደመሆኑ መረጃዎች ህብረተሰቡ ጋር የሚደርሱት ፈጥነው ነው፡፡ በመሆኑም መረጃን መሰረት በማድረግ ህብረተሰቡም አመራሩም ለተከሰተው ግጭት መፍትሄ መሻት ይኖርባቸዋል፡፡

ባለሙያዎች ግጭቶችን አስቀድሞ ለመከላከል፣ ከተከሰተ በኋላም ለመፍታት፣ ተጋላጭ ወገኖች ቀድሞ ወደነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ ለማድረግ ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት የሚሰሩበት ጊዜ ሊሆን ይገባል ይላሉ፡፡ በንቃት አዝማሚያዎቹን እያዩና እየተነተኑ ምክረ ሃሳብ ለመንግሥት የሚያቀርቡበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ባለሙያዎች ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን በየደረጃው ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ አመራሮችና የሃይማኖት አባቶች መስራት እንደሚገባቸው ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ፡፡

የአገር ሽማግሌዎች በህብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ ተቀባይነትና ተሰሚነት ያላቸው ከመሆኑም በላይ በየአካባቢው የተለያዩ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች አሉ፡፡ እነዚህን ሥርዓቶች አውጥተው ግጭትን በመከላከልና በመፍታት መንግሥትን ሊያግዙ ይገባል፡፡

የሃይማኖት አባቶች በተመሳሳይ ግጭት ካለ ቤተ ዕምነቶች የሃይማኖቱን ተልዕኮ ማስፈጸምና ስለሃይማኖታቸው ማስተማር አይችሉም፡፡ በመሆኑም ግጭትን በመከላከልና በመፍታት በኩል ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መስራት አለባቸው ሲሉ አቶ አስቻለው ይመክራሉ፡፡

መንግሥት ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊትም አስቀድሞ የመከላከል፣ በኋላም የመፍታትና የሰላም ግንባታ ሥራዎችን ለማከናወን የአሰራር ሥርዓቶችን መዘርጋት ይጠበቅበታል፡፡

‹‹ግጭትን የመከላከልና የመፍታት ሥራ የፌዴራል መንግሥት ብቻ ሳይሆን የክልሎችም ሚና ነው፡፡ በመሆኑም ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት በጋራ ሆነው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትንና የግጭት አፈታት እስትራቴጂን መዘርጋት ይኖርባቸዋል›› ነው አቶ አስቻለው የሚሉት፡፡ በግጭቱ ተዋናይ የሆኑ የህብረተሰብ አካላትን መለየትና ለህግ በማቅረብ እንዲጠየቁ ማድረግም አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ እንደሚሉትም፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በቅርቡም በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ ክልሎች መካከል የተከሰቱትን በሰላም ለመፍታት ችግሩ የተነሳበትን ምክንያት ጊዜ ወስዶ ማጥናት ዋና የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን እንደሚገባም ይናገራሉ፡፡

ችግሮች ለምን ተደጋግመው እንደሚነሱ፣ ሲነሱም መጀመሪያ መወሰድ ስላለበት ርምጃ ፣ በዘላቂነትም እንዲህ ዓይነት ችግሮች እንዳይከሰቱ በቂ ጥናት ላይ ተመስርቶ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ ክልሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት የሰው ህይወት አልፏል፣ ዜጎች ከሚኖሩበት ቦታ ተፈናቅለዋል፡፡ አሁን መደረግ ያለበት የችግሩ ምንጭ ምን እንደሆነ ጊዜ ወስዶ ማጥናት፣ ሙያዊ ትንተና መስራትና መፍትሄ መስጠት ነው፡፡ ከሚኖሩበት ቦታ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቦታቸው የመመለሱ ሥራም ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ወደ ቦታቸው ከተመለሱ በኋላም በህዝቦቹ መካከል ዘላቂ ሰላምና አብሮነታቸው እንዲቀጥል ማድረግ ትኩረት የሚያሻው መሆኑን ይናገራሉ መጋቢ ዘሪሁን፡፡

አገሪቱ አሁን እያደገች ትገኛለች፡፡ በእስካሁን ሂደት በህዝቦች መካከል ለዘመናት የዘለቀ አብሮነትና መተማመን አለ፡፡ ይህንን መልካም እሴት ማንም ሊሸረሽረው አይገባም፡፡ አልፎ አልፎ የሚነሱ ችግሮች ዋጋ እያስከፈሉ በመሆናቸው ትኩረት በመስጠት መፍትሄ ማስቀመጥ ይገባል፡፡

ችግሩ ዕድገት የወለደው ከሆነም ባግባቡ ማየትና መፍትሄ ማበጀት ይገባል የሚሉት መጋቢ ዘሪሁን፤ አንዳንድ አገሮች በዕድገት ላይ በነበሩበት ጊዜ ተመሳሳይ ችግሮች እንደተስተዋለባቸው ያስታውሳሉ፤ የእነርሱ ተሞክሮ እንደሚያሳየው የማደግና የመጠቀም ፍላጎት፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ሥራ አጥነት ምናልባት ለችግሩ ምክንያት ከሆነም ጉዳዩን በአግባቡ መያዝ ይገባል፡፡

ከአመራርና ከአስተዳደር ጉድለትና በተለያየ ፍላጎት ተገፋፍተው በህዝቦች መካከል አለመተማመን እንዲፈጠርና ወደ ግጭት እንዲያድግ ሆን ብለው የሚሰሩ አካላት ካሉም በጥናት መለየት እንዳለበት በመጠቆም፤ የአመራር ክህሎት የሌላቸውና የራሳቸውን በደል ለመሸፈን ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚሰሩ አካላት ካሉም በተመሳሳይ መልኩ በጥናት ላይ ተመስርቶ ተገቢ የመለየት ሥራ መስራት ያስፈልጋል ይላሉ መጋቢ ዘሪሁን፡፡

መጋቢ ዘሪሁን፤ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መሰረታዊ መብቶች መከበራቸውን፣ ባህሎችና ሃይማኖቶች ካለ ልዩነት ማራመድ እንዲቻል ህገ መንግሥታዊ እውቅና መሰጠቱን ይጠቁማሉ፡፡ ልዩነትን እያጠበቡ፣ በህዝቦች መካከል ያለውን ታሪክና አብሮነት የሚያጎለብቱና አንድነቱን የሚያጠናክሩ ሥራዎች መሰራት እንደሚኖርባቸው፣ ያምናሉ፡፡

የሃብት ክፍፍል ጥያቄ ሆኖ ከቀጠለ፣ የድንበር ጉዳይ ካለ ለግጭት ምክንያት ሊሆኑ ይችላል፡፡ ግን አሁን ባለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ችግሮችን ልንፈታቸው የሚገባው በውይይትና በድርድር ነው የሚለውን ዘመናዊ አመለካከት መያዝ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡

መጋቢ ዘሪሁን፣ አመራሩ ግጭት ከሚያስነሱ አመለካከቶችና አስተሳሰቦች መራቅ አለባቸው፡፡ የትኛውም አመራር ከእንደዚህ ዓይነት ተግባር ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም፡፡ ለሰው ልጅ ጥፋትና እልቂት የሚሰራ ግለሰብም ይሁን ቡድን የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር በሰውም በእግዚአብሄርም ዘንድ ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም ሲሉም ይገልጻሉ፡፡

ለፍተው ጥረው የሚያድሩ ዜጎች፣ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የገቡና የተመረቁ ወጣቶችን በተለያዩ አሳሳች መረጃዎችና አካሄዶች ለመምራት የሚደረገው ነገር መቆም አለበት፡፡ የአመራር ትልቁ እርካታ ሊሆን የሚገባው ለሰው ልጅ ሰላምና ደስታ ሲሰራ መሆን ይኖርበታል ሲሉም ይመክራሉ፡፡

የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ላይም ትኩረት ማድረግ ተገቢ መሆኑንና በተለያዩ ድረ ገጾች የመጠቀም ሁኔታ ጥንቃቄ እንደሚጠይቅ በመግለጽ ድረ ገጾቹን ለመልካም ሥራ በማዋል የህዝቦች ግንኙነት እንደ ድርና ማግ እንዲተሳሰር ማድረግ፣ እንደሚያስፈልግም ነው መጋቢ ዘሪሁን የሚናገሩት፡፡

የመገናኛ ብዙሃንን ለአብሮነትና ለዕውቀት ሽግግር ማዋል ብልህነት ነው፡፡ ትግበራው በተቃራኒው ከሆነና እንደ ተራ ሸቀጥ የሀሰት ወሬዎችን በማመንጨት ለማሰራጨት ከዋለ በዜጎች ህይወት ላይ አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ ይላሉ፡፡ ሆን ብለው አደናጋሪ መረጃዎችን መልቀቅና መርዛማ መልዕክቶችን ማስተላለፍ በሰውም ሆነ በእግዚአብሄር ዘንድ ተጠያቂ ከመሆን አያድንም፡፡ በመሆኑም አጠቃቀሙ መስመር መያዝ ይኖርበታል ሲሉም ያሳስባሉ፡፡

ህብረተሰቡም እውነትን መለየት ይኖርበታል የሚሉት መጋቢ ዘሪሁን፤ የተባለ ነገር በሙሉ እውነት ነው ብሎ ማሰብ የለበትም፣ ጊዜ ወስዶና በትዕግስት ጉዳዩን መርምሮና ተወያይቶ መወሰን ጠቃሚ ነው ይላሉ፡፡ በተለይም በክልሎች በድንበር አካባቢ ያሉ ዜጎች በከተማ ካለው ህብረተሰብ የበለጠ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋና በጋብቻ የተሳሰሩ እንደመሆናቸው ምንም ኃይል ቢመጣ ሊለያቸው ስለማይችል እንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴን በትዕግስት ማየት አስፈላጊ ነው ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡

መንግሥት ሆን ብለው ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ የሚያደርጉ አካላት ተጠያቂ ለማድረግ የጀመረው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠልና ፈጥኖ ወደ ትግበራ መግባት ይኖርበታል፡፡ ትልቅ ጉዳዮች የሚሆኑት ትንንሽ ነገሮች እየተደመሩ በመሆኑ በህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ማግኘት አለባቸው፡፡ በመሆኑም ወደ ሌላ ሥራ መገባት ያለበት ትንሽ የተባለችውን ችግር ፈትቶ ነው ሲሉም ያሳስባሉ፡፡

በየትኛውም ደረጃ በመንግሥት፣ በሃይማኖት ተቋማትና በልዩ ልዩ አደረጃጀቶች የተቀመጡ አመራሮች ጊዜ ሳይሰጡ በእያንዳንዷ ቀን ችግርን መፍታት ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ላይ ሌት ተቀን በመስራት ችግሮችን መፍታት፣ አቅም በፈቀደ መጠን ጥያቄዎችን መመለስ ያስፈልጋል፡፡ አገሪቱ እያደገች እንደመሆኑ ዕድገት ውስጥ ግጭቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ ነው የሚሉት፡፡ ግን አለመግባባቶች ወደ ግጭት እንዳያድጉ መከላከልና ማስተማር አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡

አሁን የተፈጠረውን ችግር ከስር መሰረቱ መፍታት ካልተቻለ እንደገና ተመልሶ መምጣቱ አይቀርም ሥራውም ለማንም የሚተው መሆን የለበትም፡፡ ተግባሩ የሁሉም ድርሻ በመሆኑን መረባረብ ይገባል፡፡ ለብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት፣ ለልማት፣ ለሰላም፣ ለአብሮነት የሁሉም ርብርቦሽ ያስፈልጋል ይላሉ መጋቢ ዘሪሁን፡፡

ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦችና የሃይማኖት እኩልነት የተከበረባት አገር ናት፡፡ ስለዚህ ተረጋግቶ ችግሮችን መፍታት የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ህብረተሰቡም ለሰላም መስፈን የሚጥሩ የህዝብ አገልጋይ መሪዎች እንዳሉ ሁሉ መሰሪ መሪዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ በንቃት በመከታተል ነጥሎ ደም አፋሳሽና ህይወት እንዲጠፋ የሚሰሩ አካላትን መታገል ይገባዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በአገሪቱ ውስጥ ትልቅ ስፍራ አላቸው፡፡ ይህ በሌሎች አገሮች የማይገኝ ትልቁ እሴት ነው፡፡ ሰሞኑን በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል መካከል እንደገጠመው ዓይነት ችግር ሲገጥም ከእግዚአብሄር የተሰጣቸውን የመደመጥና የመሰማት አቅማቸውን ተጠቅመው ህዝቡን መምከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ በቀዳሚነት ፈጣሪ እንዳዘዛቸው የሰላም መልዕክተኛ በመሆን ማስታረቅና ማስማማት ይኖርባቸዋል ይላሉ፡፡

ህዝቡ የሃይማኖት አባቱን የሚሰማ፣ የአገር ሽማግሌዎችንም የሚታዘዝ ነው፡፡ ይህ ለአገር ሰላምና ልማት ትልቅ ሃብት እንደመሆኑ የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ትልቅ የሰላም ሥራ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ወንጀል የሰሩ ሰዎች ከተጠያቂነት እንዳያመልጡና ፍትህ እንዳይዛባ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

የተጀመረው የአገር ልማትና የሰላም ግንባታ መቀጠል አለበት፡፡ ድህነትና ኋላ ቀርነት አሁንም ገና ያልተሻገርነው ትልቅ አጀንዳ ነው የሚሉት መጋቢ ዘሪሁን፤ በቀጣይነት ሁሉም በመረባረብ በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ኢትዮጵያ በሰላም ጉዳይ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ምሳሌ የምትሆን አገር መሆኗ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ሰሞኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በጽህፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ ከወሰን ጋር ተያይዘው በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች በውስጣዊ ችግር ሳቢያ የተከሰቱ መሆናቸውን አምኖ በየደረጃው ያለው አመራር ውስጡን ሊፈትሽ ይገባዋል፡

በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ይከሰቱ እንደነበር ጠቁመው፤ በቅርቡ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ብሄራዊ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ወራትን ያስቆጠረ ግጭት መፈጠሩን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ‹‹ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እየተፈታ ነው ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ከፋ ችግር አምርቶ የዜጎች ህይወት እንዲያልፍ ምክንያት መሆኑን እና ዜጎች ከአካባቢዎቻቸው ተፈናቅለዋል›› ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

ይህን መሰሉ ግጭት የፌዴራል ሥርዓቱን ዓላማና መርህ እንዲሁም የህዝቦችን ዘላቂ ፍላጎትና ራዕይ የሚቃረን መሆኑን በመግለጽም፤ ድርጊቱ በአፋጣኝ መቆም አለበት ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ከወሰን ጋር በተያያዘ የተፈጠሩት ችግሮች ትክክለኛ መንስኤዎች ምን እንደሆኑ ወደፊት ተጣርቶ እንደሚገለጽ በመጠቆም፤ የዜጎችን ህይወት እስከመቅጠፍ የደረሱት ሁኔታዎች አመራሮቹ ሊያስቀሯቸው የሚችሏቸው እንደነበሩም ነው የተናገሩት፡፡ በመሆኑም የችግሩን መንስኤ ወደ ውስጥ ለመመልከት፣ ችግሩንም ለዘለቄታው ለመፍታት መረባረብ እንደሚገባም ዶክተር ነገሪ ገልጸዋል፡፡

እንደ ኃላፊ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ አዋሳኝ ክልሎች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት እየሞከሩ ናቸው፡፡ ሆን ብለው አደናጋሪ መረጃዎችን በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች በመልቀቅ በህዝቦች መካከል ግጭቶችን ለማባባስ አልመው የሚሰሩ አካላትም ከአፍራሽ ተግባራቸው ሊታቀቡ ይገባል፡፡

 

ዘላለም ግዛው

 

 

Published in ፖለቲካ

ለዘርፉ ዋና ግብዓት የሆነው ጥሬ ቆዳ ዋጋ ወጥ አለመሆኑና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በከፍተኛ መጠን መውረዱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በርካታ ወገኖችም ገዢ እየጠፋ የሚጣለው ጥሬ ቆዳ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪው አቶ ኤልያስ ሲራጅም ይህን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ አቶ ኤልያስ ከአራት ዓመት በፊት ጥሬ የበግ ቆዳ በ120 ብር ገዝተው እስከ 138 ብር ለመርካቶ ነጋዴዎች ያስረክቡ ነበር። በቅርቡ ለአረፋ በዓል ወደ ደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አምርተው እንደነበር የሚናገሩት አቶ ኤልያስ ለበዓሉ የገዙትን የበግ ቆዳ የሚገዛቸው አጥተው መጣላቸውን ያስታውሳሉ።

የኢትዮጵያ ጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ አባተ እንደሚያመለክቱት፤ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ጥሬ ቆዳና ሌጦ ዓለም አቀፍ ተፈላጊነት ነበረው፡፡ የበግና የፍየል ጥሬ ቆዳ ከቡና በመቀጠል ትልቁ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ያስገኝ ነበር፤ በጥሬ ቆዳ አቅራቢነት ንግድ የሚሰማሩ ነጋዴዎችም የገንዘብና ሌሎች የማበረታቻ ድጋፎች ይደረግላቸው ነበር፡፡ ይህ አሠራር ነጋዴውን የሚያነሳሳ እንዲሁም ምርት እንዳይባክን ሲያግዝም ቆይቷል።

አሁን ባለው ሁኔታ የምርት ዋጋ ከመውረድ አልፎ ጥሬ ቆዳ የሚጣልበት ደረጃ ላይ መደረሱን የሚናገሩት አቶ ብርሃኑ፣ ፋብሪካዎችም ነጋዴዎች የሚያቀርቡላቸውን ጥሬ ቆዳ የሚረከቡት በዱቤ ግዢ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ለአቅራቢዎቹ በወቅቱ ክፍያው ስለማይፈጸም የሚሰበስቡትን ቆዳ ለመቀነስ መገደዳቸውን ያመለክታሉ።

ፋብሪካዎቹ በከፊል ያለቀላቸውን ምርቶች ወደ ውጭ ሲልኩ የሚባክን ምርት አልነበረም፤ አሁን ያለቀለት የቆዳ ምርት ብቻ እንዲላክ በመደረጉ ለዋጋ መውረድና የምርት ብክነት ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ያብራራሉ።

አቶ ብርሃኑ እንደሚሉት፤ የአገር ውስጥ የቆዳ ፋብሪካዎች ዘመናዊ የምርት ቴክኖሎጂ የላቸውም። የካፒታል ውስንነትና የአስተዳደር አቅም ማነስም ምርቶቻቸው በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ እንቅፋት ሆኗል። በዚህም ሳቢያ ፍጆታቸው ውስን ነው። ይህም ከሀገር ውስጥ የሚያቀርበው ጥሬ ቆዳ ገዢ እንዲያጣና በሂደት ዋጋው እንዲያሽቆለቁል በማድረግና ኪሳራ እያስከተለ ነው።

እንደ አቶ ብርሃኑ ማብራሪያ፤ ፋብሪካዎች ባላቸው የአቅም ውስንነትና በሚያነሱት የጥራት ችግር ለብክነት የተዳረገው የሀገሪቱ ጥሬ ቆዳ እና ሌጦ ከእዚህ ችግር እንዲወጣ ለማድረግ የሚያስችል አማራጭ እንዲፈለግ ማህበሩ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል፡፡

በቁም እንስሳት ሀብቷ ከአፍሪካ በቀዳሚነት የምትታወቀውና ከዓለም የመጀመሪያዎቹ አስር ሀገራት ውስጥ የምትመደበው ኢትዮጵያ በ2009 በጀት ዓመት 124 ሚሊዮን ስኩዌር ፊት(ጫማ) ያለቀለት ቆዳ ማምረቷን የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት መረጃ ይጠቁማል።

የኢንስቲትዩቱ የእቅድ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ብርሃኑ እንደሚሉት፤ ሀገሪቱ ከዘርፉ እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር የማግኘት እምቅ አቅም አላት። በሀገሪቱ 31 ያለቀለት ቆዳ አምራች ፋብሪካዎች ይገኛሉ። ፋብሪካዎቹ 20 ሚሊዮን ጥሬ ቆዳና ሌጦ ለምርት ግብአትነት ይጠቀማሉ።

የኢንስቲትዩቱ የገበያ ልማት ዳይሬክተር አቶ አንቲገን ከበደ የጥሬ ቆዳ ዋጋ ተቀያያሪና ወቅትን ተንተርሶ ከፍና ዝቅ የሚል ነው ይላሉ።

በበዓላት ሰሞን ጥሬ ቆዳ በብዛት እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ይህም ለዋጋ መቀነስ አንድ ምክንያት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡በሌላ በኩል የዓለም ገበያ ዋጋ ሲቀዛቀዝ የአገር ውስጥ የቆዳ ፋብሪካዎች የሚገዙትን ጥሬ ቆዳ እንዲቀንሱ ያስገድዳቸዋል ሲሉ ያብራራሉ።

የአገሪቱ የጥሬ ቆዳ ጥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣት፣ የቆዳ ፋብሪካዎች የገንዘብ አቅም ጥሬ ቆዳ እንዳያከማቹ ማድረጉንም ይጠቁማሉ ፡፡ ይህም በተዘዋዋሪ መንገድ አቅራቢዎች የገዙትን ጥሬ ቆዳ እንዲያከማቹ የሚያደርግ እንደሆነ ይናገራሉ።

ባለፈው ዓመት የጥሬ ቆዳ ዋጋ ቀንሶ እንደነበር እሳቸውም ይጠቅሳሉ፡፡ይህን ችግር ለመፍታት ኢንስቲትዩቱ ከኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ድርጅት ጋር በመተባበር ፋብሪካዎች የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙበትንና ከአቅራቢዎች ቆዳ የሚረከቡበትን ዕድል መፍጠሩን ይገልጻሉ።

እንደ አቶ አንቲገን ገለጻ፤ አሁን በቆዳ አቅራቢዎች ዘንድ ያለው የጥሬ ቆዳ ክምችት ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ኢንስቲትዩቱ የዳሰሳ ቅኝት እያደረገ ይገኛል፡፡በሚሰበሰበው መረጃ ላይ በመመርኮዝ ለፋብሪካዎችም ተመሳሳይ እገዛ ሊደረግላቸው ይችላል።

የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ድርጅት ጥሬ ቆዳ በመግዛት «ዌይትብሉና ፒክል» ተብለው የሚታወቁት በከፊል ያለቀላቸው የቆዳ ምርቶችን ያዘጋጃል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ፋብሪካዎች ቆዳ ሲፈልጉ ከድርጅቱ እንደሚገዙም ይጠቁማሉ።ይህም የጥሬ ቆዳ መበላሸትንና አላስፈላጊ ክምችትን መቀነስ ያስችላል።

በእንስሳትና ዓሳ ሃብት ሚኒስቴር የጥሬ ቆዳና ሌጦ ግብይት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ፈቃዱ መርሻ እንደሚሉት፤ በዓለም ገበያ የቆዳ ውጤቶች ዋጋ መውረድ ፋብሪካዎች ጥሬ ቆዳና ሌጦ ከመግዛት እንዲቆጠቡ ያደርጋል።ፋብሪካዎች በአገር ውስጥ የሚቀርበው ቆዳ በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊ ምርት ለማምረት የሚያስችል ጥራቱን የጠበቀ አይደለም የሚል ቅሬታ እያቀረቡም ናቸው።

የጥሬ ቆዳና ሌጦ ግብይት አዋጅ ግብይቱን ለማሳለጥና ሰንሰለቱን ለማሳጠር በሚረዳ መልኩ እንዲሻሻል ለማድረግ የተሻሻለ ረቂቅ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እየታየ ሲሆን፣በቅርቡም በረቂቁ ላይ የቆዳና የጥሬ ቆዳ ፋብሪካዎች የሚነጋገሩበት የጋራ የውይይት መድረክ ይካሄዳል።

በጥራት ላይ ያለው ችግር ከእርድ በፊት ፣ እንስሳት የተመጣጠነ መኖ ባለማግኘታቸው፣ በበሽታ ተይዘው ሳይታከሙ ከቀሩና በቆዳቸው ላይ በስለት በሚደረግ ምልክት የሚፈጠር ሊሆን እንደሚችል ባለሙያው ገልጸው፣ እንስሳት በእሾህና በሌሎች ነገሮች ቆዳቸው ሲወጋ ጥራቱ ሊጓደል እንደሚችልም አብራርተዋል።

እንደ አቶ ፍቃዱ ገለጻ፤ ይህን ችግር ለመፍታት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አርብቶና አርሶ አደር የኀብረተሰብ ክፍሎች ዘመናዊ የአረባብ ዘዴ እንዲከተሉ ሰፊ የኤክስቴንሽን ሥራ እያከናወነ ከመሆኑም በላይ በእርድ ወቅት የሚያጋጥም የቆዳ ጥራት መጓደልን ለመቀነስ በቄራዎች፣በከተሞችና በገጠር ቀበሌዎች እርድ ከሚፈፅሙ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችና ሕብረተሰቡ ጋር ይሰራል።

ከእርድ በኋላ በቆዳ ማጓጓዝ፣ በክምችት ወቅት በመጋዘን የሚያጋጥም የጥራት መጓደልን ለመቀነስም ቆዳ አቅራቢዎች በጥንቃቄ መስራት ይኖርባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተሩ አቶ መላኩ ታዬ ድርጅቱ እሴት ጨምሮ በከፊል ያለቀለት ቆዳ ለትልልቅ፣አነስተኛና መካከለኛ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ ጥሬ ቆዳ በብዛት እየገዛ እንደሚገኝ ይናገራሉ። በዚህም ገዢ ባለመኖሩ ጥሬ ቆዳ ለብክነት እየተዳረገ ነው በሚለው ሃሳብ አይስማሙም። በተያዘው ዓመትም ማንኛውም የጥሬ ቆዳና ሌጦ ከሁሉም የጥሬ ቆዳ አቅራቢዎች እንደሚገዛ በመጥቀስ።

ዳይሬክተሩ የጥሬ ቆዳ ዋጋ ከፍና ዝቅ ማለት የዓለም የገበያ ሁኔታ የሚያስከትለው ነው የሚለውን ሃሳብ ይጋሩታል። ነጋዴዎች እጅ ላይ ሳይገባ ሕብረተሰቡ በየአካባቢው የሚስቀረውና በግንዛቤ እጥረት የሚጣል ካልሆነ በስተቀር ገዢ በማጣት ምክንያት የሚባክን ጥሬ ቆዳ አለመኖሩን ይናገራሉ።

ድርጅቱ የዓለም አቀፍ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ዋጋን መሰረት በማድረግ የዋጋ ቅኝት እንደሚያደርግ የሚያስረዱት ዳይሬክተሩ ይህም አቅራቢዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ባይ ናቸው።

 

በሪሁ ብርሃነ

 

Published in ኢኮኖሚ

ፕሬዚዳንቱ የዕድሜ ገደብ ድንጋጌውን እንዲያከብሩ ግፊት በርትቶባቸዋል ፤

 

የዩጋንዳ ህገ መንግሥት አንቀፅ 102 አንድ ሰው ፕሬዚዳንት ለመሆን ብቁ ነው የሚያሰኘውን የእድሜ ጣሪያ ገደብ በግልፅ አስቀምጧል። በህገ መንግሥቱ መሰረትም ማንኛውም ሰው አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት ለማስተዳደር ብቁ ነው የሚባለው እድሜ ከ 35 ዓመት በላይ አሊያም ከ 75 ዓመት በታች ሲሆን ብቻ ነው።

የወቅቱ የዩጋንዳ ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ አሁን 73 ዓመታቸው ነው። ዩጋንዳም ቀጣዩን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እ..አ በ2021 ታካሂዳለች። ያኔ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት 76 ዓመት ይሆናቸዋል። በዚህ ስሌት ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ በስልጣን መቆየት የቻሉት ሙሴቬኒ በምርጫው ለመወዳደር ይቸገራሉ ማለት ነው። ይህ እንዳይሆን ከተፈለገና ሰውየው በምርጫው እንዲወዳደሩ ለማድረግ ታዲያ የአገሪቱን ህገ መንግሥት መለወጥ የግድ ይላል።

ሙሴቬኒና ፓርቲያቸው በቀጣዩ ምርጫ ለማወዳደር ፍላጎት አላቸው። ለእዚህም የገዢው ኤን አር ኤም ፓርቲ አባላት መሪያቸው በቀጣዩ ምርጫ እንዲወዳደሩ ለማስቻል እድሜን በሚመለከት በህገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ህገ ደንብ ለማሻሻል መንደርደር ጀምረዋል። ለእዚህም እንዲረዳቸው የህግ ረቂቅ ቀምረዋል።

ይህ ረቂቅ አዋጅ እድሜ አንድን ግለሰብ ከስልጣን በተለይም በፕሬዚዳንትነት አገሪቱን ከመምራት ሊያግድ አይገባም፤ እናም በህገ መንግሥቱ የእድሜ ገደብ መቀመጡ አግባብ አይደለም የሚል አቋም ሲያንጸባርቁ የቆዩ አካላትን በእጅጉ አስፈንድቋቸዋል።

እንደ እሳቤው የደጋፊዎች እምነት፤ በአገሪቱ ህገ መንግሥት የእድሜ ገደብ መስፈሩ በራሱ አድሎአዊነት ነው። እድሜያቸው ከ75 በላይ የሆኑ ሰዎች ደካማና አስፈላጊ አይደሉም ብሎ ማሰብ ነው። አሁን ላይ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እድሜያቸው 75 በላይ የሆኑ ግለሰቦችን በመቅጠር ላይ ናቸው። ሙሴቬኒ እድሜያቸው 75ና ከዚያ በላይ ሆነ ማለት መምራት አይችሉም ማለት አይደለም።

ሰውየው ዘላለማዊ አይደሉም፤ ማለፋቸውም አይቀርም። አገሪቱና ህገ መንግሥቱ ግን ዘላቂ ናቸው።

በቀጣዩ ምርጫ ምናልባትም ሊሸነፍ እንደሚችል ማሰብ አግባብ ነው። እናም ሰውየው በስልጣን እንዳይቆዩ በሚል የሚንፀባረቅ የግል ፍላጎት ጉዳት አለው። ነገ ሌሎች እድሜያቸው 75 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ፕሬዚዳንቶች ወደ ስልጣኑ እንዳይመጡ ማድረግ አግባብ አይደለም። ስለዚህም እድሉን ልንስጣቸው ይገባል የሚል አቋም ይዘዋል። በመሆኑ «ህገ መንግሥቱ ሊሻሻል ይገባል» ይላሉ።

የረቂቅ ህገ ማሻሻያው ተቃዋሚዎች በአንፃሩ አንድ ሰው እድሜ ልኩን በስልጣን እንዳይቆይ ብቸኛው አጥር ይህ አንቀፅ ነው። ሰውየውን እድሜ ልክ በስልጣን ለማቆየት የህገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ ፍፅሞ አይሞከርም፤ ህገ አንቀፁ ተሻሻለ ማለት ከሰላሳ ዓመት በላይ አገሪቱን ማስተዳደር የቻሉትን ሰው እድሜ ልክ እንዲገዙ በገዛ ፈቃድ መወሰን ነው፤ እናም የህገ መንግሥቱን አንቀፅ ትነኩና እንተያያለን የሚል አቋም ይዟል።

ይህ የድጋፍና የተቃውሞ መነሾ የሆነ የአገሬው ህገ መንግሥት የእድሜ ገደብ ህገ አንቀፅና የሙሴቬኒ የእድሜ ጉዳይ ታዲያ እስከ አገሬው ፓርላማ ዘልቋል። የማሻሻያው ደጋፊዎች የእድሜ ገደቡን ለማሻሻል የሚያስችለውን ረቂቅ ህግ ለፓርላማው አመንጭተዋል። የሀገሪቱን ፕሬዚዳንት የስልጣን ዕድሜ ጣሪያ ለመወሰን የተሰበሰበው የዩጋንዳ ፓርላማም ባለመስማማት ተበጥብጦ ውሏል። የፕሬዚዳንቱ እድሜ መዘዝም አገሪቱ ነፃነቷን ከተቀዳጀች ብዙም ሳይርቅ እ..1962 እንደተመሰረተ የሚነገርለት የአገሬው ፓርላማ የለየለት የእርስ በእርስ ጠብ እንዲያስተናግድ ምክንያት ሆኗል።

በዋና ከተማዋ ካምፓላ በሰላማዊ ሰልፉ የተገኙት ተቃዋሚ ሰልፈኞች፤ መሪውና ፓርቲያቸው መብታችንን ወስደውብናል፤ እናም ይህን መብታችንን ማስከበር ይኖርብናል። ለህገ መንግሥታችን ሉአላዊነት መከበር እንታገላለን ሲሉ ተደምጠዋል። ወቅታዊውን ህገ መንግሥት ማሻሻያ በሚመለከት ታዲያ መገናኛ ብዙኃንና የተለያዩ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኞች፤ በቀውሱ ላይ የግል ምልክታቸውን በማስቀመጥ ላይ ይገኛሉ።

የወርልድ ቪውስ ዘገባ፤ሙሴቬኒ በስልጣን ለመቆየት ካላቸው ጥልቅ ፍላጎት በመነጨ በመንበረ ስልጣናቸው ዘላለም ለመቆየት የሚያስችላቸውን ፈቃድ ለማግኘት የአገራቸው ህገ መንግሥት ከቀየሩት አሊያም ካሻሻሉት እንደ ዚምባብዌ፤ ብሩንዲ፤ ሩዋንዳ፤ ኮንጎ ከመሳሰሉ አገራት መሪዎች ተርታ የሚሰለፉ መሆናቸውን ያትታል።

እንደ መገናኛ ብዙኃኑ ዘገባ፤ ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ ወደ ስልጣነ መንበሩ የመጡት እ..1986 ነው። ምንም እንኳን የአገሪቱ ህገ መንግሥት አንድ ፕሬዚዳንት ከሁለት የስልጣን ዘመን በላይ መቆየት እንደሌለበት ቢደነግግም ሰውየው ግን ይህን ህገ ደንብ፤ በ2005 ሽረውታል። ይህን ማድረጋቸውም ለተጨማሪ ዓመታት በስልጣን እንዲቆዩ ፈቃድ ሰጥቷቸዋል። ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ብቻም ሳይሆን ለሶስት፤ ለአራትና ለአምስተኛ ጊዜ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲወዳደሩና አሸንፈውም በስልጣን እንዲቆዩ አስችሏቸዋል። እናም ዛሬ እንዳለፈው ሁሉ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ዳግም ህገ መንግሥቱን ለማሻሻል ጅምር ጥረቶችን ማካሄድ ጀምረዋል። ይህ ጥረታቸው ደግሞ እስክ እድሜ ማጭበርበር የሚዘልቅ እንደሆነ እየተነገረ ነው።

እንደ ኦል አፍሪካ ድረ ገፅ ዘገባና ሃጊ ማሲኮ ሀተታ፤ የሰውየው የውልደት ዘመን እ..1944 ነው። ይሁንና አሁን ላይ የሰውየውን የእድሜ ዘመን ወደ እ..1947 ለመውሰድ አንዳንድ ጨዋታዎች መጫወት ተጀምሯል። ጨዋታው በመሪው አሸናፊነት የሚቋጭ ከሆነ ደግሞ ህገ መንግሥቱን ማሻሻል ሳያስፈልግ ሰውየው በቀጣዩ 2021 እንዲወዳደሩ ፈቃድ ይሰጣቸዋል» ይላል።

ፀሃፊው ይህን ይበል እንጂ የሙሴቬኒን የልደት አሊያም የውልደት ቀን መለወጥ ቀላል አይደለም። በአግባቡ አብጠርጥሮና አጣርቶ ማግኘት ይቻላል የሚሉም አልጠፉም።

እንደ አፍሪካ ፒዲያ ድረ ገፅ ፀሃፊው ቻርለስ ኦንያንጎ ኦቦ፤ በአገሪቱ ህገ መንግሥት የተቀመጠው የፕሬዚዳንትነት የስልጣን ገደብ ዘመን በሙሴቬኒ እጅ ጠምዛዥነት እ..2005 መለወጡን ተከትሎ የተከሰተ ቀውስ ለወቅቱ የእድሜ ማሻሻያ ጥያቄ ዋነኛ ምክንያት ነው» ይላል። እንደ ፀሃፊው ሀተታም፤ ለሙሴቬኒ የህይወት ዘመን የተሰጠው የፕሬዚዳንትነት የስልጣን ገደብ ዘመን ማሻሻያ ከሰባት ዓመታት በፊት ሲሻሻል ነው።

አሁን ፕሬዚዳንቱ የሚሸጡበት ትክክለኛው ሰዓት ላይ ናቸው። ይህ እስካልሆነ ግን እንደ ቶጎ ቀውስ ውስጥ መግባት አይቀሬ ነው። የቀድሞው የቶጎ ጄነራል ስልጣን ለማስረከብ ዳተኛ በመሆናቸው 2002 የፕሬዚዳንትነት ዘመነ ስልጣናቸው የሚወስነውን የአገሪቱን ህገ መንግሥት አሻሽለዋል።

እናም እንደ ፀሃፊው ገለፃ፤ የእድሜ ገደብ ማሻሻል ማስቆም ብቻ ሳይሆን የፕሬዚዳንትነት የስልጣን ገደብ ዘመን በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ሲቻል መሰል ቀውሶችን ማስቀረት እንደሚቻል ይገልፃሉ። ምክንያቱም በመጀመሪያዎቹ ሁለት የስልጣን ዘመን ቢሮውን ለሌላ ማስረከብ ያልቻለ ግለሰብ ለሶስት አራትና አምስተኛ እስክ አስር ጊዜ እስካልተመረጠ ስልጣኑን ማስረከብ በእጅጉ ይቸግረዋል።

ከዚህ በአንፃሩ ይህን አንቀፅ ተግባራዊ ለማድረግ የምክር ቤቱ አባላት ረብጣ ገንዘብ እንደተከፈላቸው መርሳት እንደማይገባ በመግለጽ የፕሬዚዳንቱ የስልጣን ጥምና የእድሜያቸው መዘዙ በቀጣይ ብዙ ቀውሶችን እንድሚያስከትል ስጋታቸውን የሚገልፁ በርካቶች ሆነዋል።

እናም ከወዲሁ ሰውየውን የእድሜ ገደቡን እንዲያከብሩ ማግባባት አሊያም ማስገደድ የግድ እንደሚል የሚያምኑ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ዮዌሪ ሙሴቬኒ ግን የአገሪቱ ህገ መንግሥት የተቀመጠውን የፕሬዚዳንት የእድሜ ገደብ ለማሻሻል ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጅቷል ስለሚባለው የማውቀው የለም የሚል አቋም አንፀባርቀዋል። ሰውየው ይህን ይበሉ እንጂ ከጀርባ ስራቸውን እየሰሩ ለመሆኑ ምስክር ነን የሚሉም በርካቶች ሆነዋል።

ህገ መንግሥቱን መቀየር ህጋዊነት ከሆነ የአገሬው ህዝብ እድሜው የገፋም ቢሆን የሚመራውን የመምረጥ ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል የሚሉም አልታጡም።

አንድ ሰው ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በስልጣን ቆይቶ በግልፅና ፍትሃዊ ምርጫ አሊያም በእድሜ መግፋት ምክንያት ወንበሩን ለሌሎች ለማስተላለፍ ፍላጎት ካላሳየ አሊያም ለመስጠት ዳተኛ ከሆነ ብቸኛው ሰውየውን ከስልጣን የማንሳት አማራጭ አመፅ መሆኑን የሚያምኑ መበራከታቸውን ታዲያ በአብዛኞች ዘንድ ስጋት ፈጥሯል።

እናም በጉዳዩ ላይ ሃሳባቸውን የሚያጋሩ የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኞች በማጠቃላያቸው፤ዛሬ የፕሬዘዳንቱ እድሜ መዘዝ ያስከተለው የፓርላማ ድብድብ ነገ በመንግስትና ተቃዋሚዎች አሊያም በህዝቡ መካካል እንዳይሆን ከወዲሁ ለቀውሱ እልባት መስጠት እንደሚያስፈልግና አስፈላጊው ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ አስምረውበታል።

 

ታምራት ተስፋዬ

 

 

Published in ዓለም አቀፍ

 

2010 የትምህርት ዘመን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም መግቢያ መቁረጫ ነጥብ ይፋ ማድረጉን የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበራ አባተ ትናንት በቢሯቸው በሰጡት መግለጫ እንደገለፁት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በ2010 .ም በተቀመጠው የመቁረጫ ነጥብ መሰረት ወደ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የሚገቡ የ10ኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ከደረጃ 1 እስከ 5 በአጠቃላይ 591 648 ናቸው፡፡

በዚሁ መሰረትም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና የወሰዱ በደረጃ 1 እና 2 የሚሰለጥኑ የታዳጊ ክልሎችንና አርብቶ አደር አካባቢዎችን ሳይጨምር ለወንዶች 2 ነጥብ 29 እና ከዚያ በታች እንዲሁም ለሴቶች 2 ነጥብ 14 እና ከዛ በታች የመቁረጫ ነጥቡ ሲሆን ፣ ለታዳጊ ክልሎችና አርብቶ አደር አካባቢዎች ለወንዶች 2 ነጥብ 14 እና ከዛ በታች እንዲሁም ለሴቶች 2 ነጥብ እና ከዚያ በታች ሆኗል፡፡ በዚሁ ደረጃ ለሁሉም አካል ጉዳተኞች የመቁረጫ ነጥቡ 1 ነጥብ 57 እና ከዚያ በታች መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ የወሰዱ በደረጃ 3 እና 4 ገብተው የሚሰለጥኑ የታዳጊ ክልሎችንና አርብቶ አደር አካባቢዎችን ሳይጨምር ለወንዶች 2 ነጥብ 43 እና ከዚያ በላይ ለሴቶች ደግሞ 2 ነጥብ 29 እና ከዚያ በላይ ሆኗል፡፡ ለታዳጊ ክልሎችና አርብቶ አደር አካባቢዎች ለወንዶች 2 ነጥብ 29 እና ከዚያ በላይ እንዲሁም ለሴቶች 2 ነጥብ 14 እና ከዚያ በላይ መሆኑን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡ በዚሁ ደረጃ ለሁሉም ክልል አካል ጉዳተኞች 1 ነጥብ 71 እና ከዚያ በላይ ሆኗል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና የወሰዱ ወይም 12ኛ ክፍል ያጠናቀቁና በደረጃ 3 እና 4 የሚሰለጥኑ የታዳጊ ክልሎችንና አርብቶ አደር አካባቢዎችን ሳይጨምር ለወንዶች 269 እና ከዛ በታች እንዲሁም ለሴቶች 264 እና ከዛ በታች ሆኖ የመቁረጫ ነጥቡ ተለይቷል፡፡ ለታዳጊ ክልሎችና አርብቶ አደር አካባቢዎች ደግሞ ለወንዶች 249 እና ከዛ በታች እንዲሁም ለሴቶች 244 እና ከዛ በታች መሆኑ ታውቋል፡፡ የሁሉም ክልል አካል ጉዳተኞች የመቁረጫ ነጥብ ደግሞ 169 እና ከዛ በታች መሆኑ ተገልጿል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና የወሰዱ ወይም 12ኛ ክፍል ያጠናቀቁና በደረጃ 5 የሚሰለጥኑ የታዳጊ ክልሎችንና አርብቶ አደር አካባቢዎችን ሳይጨምር ለወንዶች 270 እና ከዚያ በላይ እንዲሁም ለሴቶች 265 እና ከዚያ በላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ለታዳጊ ክልሎችና አርብቶ አደር አካባቢዎች ደግሞ ለወንዶች 250 እና ከዚያ በላይ እንዲሁም ለሴቶች 245 እና ከዛ በላይ መሆኑ ታውቋል፡፡ በደረጃ 5 ለሁሉም ክልል አካል ጉዳተኞች ደግሞ የመቁረጫ ነጥቡ 170 እና ከዛ በላይ እንዲሆን ተወስኗል፡፡

2010 .ም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም የመግቢያ መቁረጫ ነጥብ መስፈርት የአካል ጉዳተኛ ዜጎችን፣ ሴቶችንና ታዳጊ ክልሎችን እንዲሁም የአርብቶ አደር አካባቢዎችን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆኑን ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡

 

አስናቀ ፀጋዬ

Published in የሀገር ውስጥ

 

በኢትዮጵያ ዛሬ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየጎለበተ የመምጣቱ ሁኔታ እርግጥ ሆኗል። አንዳች እንከን የለበትም ማለት ግን አይደለም። ይህንን በተገቢው መንገድ የመገንዘብ ችግር አሁን ላይ መንፀባረቁ አልቀረም፡፡ በእርግጥ መልካም አስተዳደር የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ካልታከለበት በመንግሥት ጥረት ብቻ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። ማንኛውም ጉዳይ ህዝብ ካልተሳተፈበት ተፈፃሚ ስለማይሆን።

በመሆኑም በመንግሥት በኩል መልካም አስተዳደርን ዕውን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉና በሂደት የሚከናወኑ ቁርጠኛ ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው መላው ህዝብም ዛሬም እንደ ትናንቱ ለተግባራዊነቱ መረባረብ ይኖርበታል።

በተለይም ቁልፍ የዴሞክራሲ ማስፈኛ ተቋማት በሚባሉት እንደ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዓይነቶችን በአግባቡ በመጠቀምና የሚፈጠሩ ችግሮችን ተከታትሎ በማሳወቅ ለመልካም አስተዳደር እመርታ መትጋት ከማንኛውም ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ነው። መንግሥት ምንም እንኳን ግዴታው ቢሆንም ሕገ መንግሥቱ በሚያዘው መሠረት ብሎም ራሱም ለዴሞክራሲ ሥር መስደድ ካለው ቀናዒ ፍላጎት በመነሳት፤ እነዚህን ተቋማት አደራጅቷል ።

ተግባራቱም በአንክሮና በሰከነ አዕምሮ ከታዩ መንግሥት ለዴሞክራሲው ግንባታ ዕውን መሆንና ላሳየው የማይናወጥ ቁርጠኝነት ሊመሰገን ይገባዋል። በስሜት ብቻ እየተገፋፉ መንግሥት በዘርፉ እያደረገ ያለውን ጥረት በፀረ ዴሞክራሲያዊነት ታውሮ ላለመቀበልና ለማጣጣል መሞከር በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም። እንዲህ ዓይነት ስንኩል አመለካከት ገንቢና ዴሞክራሲያዊ ባለመሆኑ ይህ ጭፍን እሳቤ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱ አሜኬላ እሾህ መሆኑ አይቀርም።

መልካም አስተዳደር የሚታሰበው ሥርዓቱ ተግባሩን ለማከናወን ካለው በጎ ምልከታ አኳያ መሆኑ እርግጥ ነው። ታዲያ የአገራችን ፖለቲካዊ ሥርዓትም መልካም አስተዳደርን በሂደት ለመፈፀም ቁርጠኝነት ያለው ብቻ ሳይሆን፤ መልካምና የተመቻቸ ምህዳር ጭምርም የነገሰበት ነው። ለምን ቢባል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ሥልጣን የህዝብና የህዝብ ብቻ መሆኑን በግልፅ በማስቀመጡ ነው። ሥልጣን የተገልጋዩ ህዝብ መሆኑ ደግሞ ለመልካም አስተዳደር እመርታ የራሱ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አይካድምና።

እንደሚታወቀው መልካም አስተዳደር የተግባር እንጂ የንድፈ ሐሳብ ጉዳይ አይደለም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው የመልካም አስተዳደር ተግባር ከዜጎች የዕለት ተዕለት የኑሮ ሁኔታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ፤ በአተገባበሩ ላይ የሥልጣኑ ባለቤት የሆነው ህዝብ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን አለበት። ህዝቡ በሕገ መንግሥቱ የተጎናፀፈውን ሥልጣን በአግባቡ እንዲጠቀምበት ዕድል ይፈጥራል።

ታዲያ የአገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ይህ ሁኔታ እንዲተገበር በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ችግሮችን እየተከታተሉ በማረም ለመልካም አስተዳደር ግንባታ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ከተቋቋሙት ገለልተኛ አካላት ውስጥ ለአብነት ያህል የሚጠቀሱ ናቸው።

ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እነዚህ አካላት እንዲቋቋሙ በአዋጅ ከማፅደቅ ጀምሮ ተግባራቸውንም የመልካም አስተዳደር እመርታን በሚያረጋግጥ አኳኋን እንዲፈፅሙ እስከ ማድረግ ድረስ አመቺ የሆኑ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።

እነዚህ ገለልተኛ አካላት ህዝቡ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተደነገጉትን መሠረታዊ መብቶች ተግባራዊ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ። እስካሁንም ድረስ በርካታ ህዝባዊ ጉዳዮችን በመመልከት የተጣለባቸውን ኃላፊነት አቅም በፈቀደ ሁኔታ እየተወጡ ነው። የመልካም አስተዳደር ሥራ ሂደት ነው። ምሉዕ ሊሆን በርካታ ዓመታትን ይጠይቃል። አገራችንም ካለባት የማስፈፀም አቅም ውስንነት አኳያ ተያይዞ የሚታይ ነው።

እንዲህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት ያለው የመልካም አስተዳደር ትግበራ አፈፃፀም የአቅም ውስንነትን ተሻግሮ መሻሻል እያሳየ ነው። ይህ ማለት ግን ፈፅሞ የመልካም አስተዳደር ችግር የለም ማለት አይደለም። በአስቸኳይ መፈታት ያለባቸው ችግሮች በአፋጣኝ መፍትሄ እየተሰጣቸው ነው። ሌሎችም እየታዩ በሂደት ምላሽ ያገኛሉ። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ማንኛውም የመልካም አስተዳደር ችግር በሂደት መስተካከሉ አይቀሬ ነው።

በዛሬዪቷ ኢትዮጵያ ዕውን በሆነው ባልተማከለው ፌዴራላዊ ሥርዓት መሠረት፤ ህዝቡ የፖለቲካ መሪዎቹንና ተወካዮቹን ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ደረጃ ድረስ ይሾማል፤ ይሽራል። ህዝቡ በምርጫ ካርዱ አማካይነት በቀጥታ የሥልጣን ባለቤት የሆነበት ይህ አሠራር በሥርዓቱ ውስጥ ወሣኝ ሚና ቢኖረውም፤ በህዝቡ በቀጥታ የማይመረጡና ሊመረጡ የማይችሉ አካላት መኖራቸው አይቀርም። በዚህ የአሠራር ማዕቀፍ ውስጥ የሚጠቀሱት ሥራ አስፈፃሚው፣ ሲቪል ሰርቪሱና የዳኝነት አካላት ናቸው።

እነዚህ አካላት ለመልካም አስተዳደር አተገባበር ያላቸው የማይተካ ሚና ስለሚታወቅም እንደ ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ አገር በምክር ቤቶች የሚሾሙ ወይም ለምክር ቤቶቹ ተጠሪ ይሆናሉ። ሆኖም ግን የየራሳቸው ነፃነት ያላቸው አካላት መሆናቸውን መዘንጋት አያስፈልግም። እነዚህ አካላት ህዝቡና የህዝቡ ተወካዮች በዴሞክራሲያዊ ሁኔታ መክረው ያፀደቋቸውን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ህጎች በተሟላ ሁኔታ የሚያስፈፅሙ እንዲሁም ለሁሉም ዜጋ ያለ አድልኦ ፈጣን አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን ማወቅ ተገቢ ይሆናል። እነዚህ አካላት ይህን በማድረጋቸው የህዝቡ ሉዓላዊነት መሣሪያዎች፣ አገልጋዮችና የመልካም አስተዳደር ፈፃሚዎች ከሆኑ በርካታ ዓመታትን አስቆጥረዋል።

የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓቱ የተጠቃሚው መብትና ጥቅም እንዳይሸራረፍ እንዲሁም ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። ይህ ተግባርም መንግሥት በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን መተኪያ የሌለው ድርጊት መሆኑን እንደሚያምንና በቁርጠኝነት ለመተግበርም በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀሱን የሚያመላክት ነው። ከዳኝነት ሥርዓቱ ጋር በተያያዘም ህዝቡ በተወካዮቹ አማካይነት ያፀደቀውን ሕገ መንግሥትና ይወክሉኛል ባላቸው አካላት በኩል የሚወጡ ህጎችን በትክክል መተርጎሙ በዚህ መሠረትም አቅም በፈቀደ መጠን ለባለ ጉዳዩ ፈጣንና ትክክለኛ ፍትህ ያለ አንዳች አድልኦ መስጠቱ ሥር እየሰደደ ነው።

ታዲያ እዚህ ላይ ከአገራችን ለጋ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት አኳያ ሲቪል ሰርቪሱም ይሁን የዳኝነት ሥርዓቱ ፍፁማዊ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ማለት አዳጋች ነው። ዴሞክራሲው ገና ጅምር በመሆኑ ብሎም ካለፉት ሥርዓቶች የወረስናቸው የተለያዩ አመለካከቶች እንቅፋት መፍጠራቸው አይቀሬ ነው። ይሁንና መንግሥት ይህን ሁኔታ ለመቅረፍ ችግሮቹን በአፋጣኝ ለመፍታት በርካታ ርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።

የሰለጠነ የሰው ኃይልን በመፍጠርና ሥርዓቱ የሚፈልገውን የሥራ አስፈፃሚና የህግ ተርጓሚ አካላትን ዕውን ለማድረግ የማስፈፀም አቅምን በመገንባት ረገድ የወሰዳቸው ወሣኝ ርምጃዎች ተጠቃሽ ናቸው። የሰው ኃይልን በተግባር ሂደት የማብቃት፣ አሠራርና አደረጃጀትን ለማሻሻል የሚያስችል የሲቪል ሰርቪስና የፍትህ አስተዳደር ማሻሻያ ተቀርፆም ወደ ተግባር በመግባት ከፍተኛ ውጤት ተገኝቶበታል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ሊያሠራ የሚችልና ወደፊት የሚጎለብት የማስፈፀም አቅምን በሲቪል ሰርቪሱና በዳኝነት ሥርዓቱ ውስጥ ለመገንባት ተችሏል።

በጥቅሉ ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ተግባራት ተከናውነው ውጤት ተገኝቶባቸዋል። ይህን ዕውን ለማድረግም መንግሥት በየደረጃው ተጨባጭ ርምጃዎችን ወስዷል። በርካታና የተወሳሰቡ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ካለፉት ሥርዓቶች ቢረከብም በየደረጃው ተገቢ ናቸው ተብሎ በታመነባቸው ላይ ርምጃዎች ተወስደዋል፤ በመውሰድ ላይም ይገኛል። መልካም አስተዳደር – ዛሬም ቀዳሚ ትኩረት ተሰጥቶታልና!

 

አባ መላኩ

 

 

Published in አጀንዳ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።