Items filtered by date: Wednesday, 04 October 2017

 

የኢትዮጵያ አትሌቲ ክስ ፌዴሬሽን በአገር አቀፍ ደረጃ በአትሌ ቲክስ ስፓርት ከፌዴ ራል እስከ ቀበሌ ድረስ በቅንጅት መሥራት ባለመቻሉ ተተኪ አትሌ ቶችን ማፍራት እንዳልቻለ ገለፀ፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ የአትሌቲክስን ስፓርት ለማስፋፋትና ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር በተዘጋጀ መድረክ ላይ እንደተናገሩት ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር እና አሠራር ቅንጅት የጎደለው በመሆኑ ተተኪ አትሌቶች ወደ ዓለም አቀፍ ሩጫ ውድድር እንዳይመጡ አድርጓል ፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ በየክልሉ ያሉ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለስፖርቱ ትኩረት ሰጥተው አለመሥራታቸው፤ የውሸት ሪፓርት ማቅረብ ችግር፤ ቅንጅታዊው አሠራር አለመዘርጋት፤ ለአትሌቶች ትክክለኛና ወጥ የሆነ ሥልጠና አለመስጠቱ፤ ዕድሜን መሰረት ያደረገ የሰልጣኞች ምልመላ አለመደረጉና የዕድሜ ማጭበርበር ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንቅፋት ሆነዋል፡፡

በክልሎች፤ በክበባት፤ በፕሮጀክቶች እና በትምህርት ቤቶች ተገቢው የሥልጠና ቁሳቁሶች አለመኖራቸውን ጠቅሰው በ2010 .ም እነዚህን ችግሮች በመፍታት በአትሌቲክሱ ስፖርት ላይ የሚታየውን የተተኪ አትሌቶች ጉድለት የመሙላት ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡

የሚመለከታችው አመራሮችና ባለድርሻ አካላትም የመወዳደሪያ መሣሪያዎችን ማሟላት፤ የአሠል ጣኞችን ሙያ ማሳደግ፤ ምልመላ ሲካሄድ ትክክለኛ ዕድሜ ላይ መሰረት አድርገው መሥራት አለባቸው ብለዋል ሻለቃ አትሌት ኃይሌ፡፡

በአገሪቱ አትሌቲክስን ለማስፋፋት የተዘረጋውን የስልጠና እና ውድድር የልማት ተግባራት ግልፅ፣ ቀልጣፋ እና ውጤታማ ማድረግና ማስቀጠል የሚቻለው የአደረጃጀት እና የቅንጅት ሥራዎችን በአግባቡ ማከናወን ሲቻል ነው። የአትሌቲክስ ስፓርት እድገት መጀመርያው በስፓርት ተሰጥኦ እና ብቃት ያላቸውን አትሌቶች አስሶ ከማገኘት የሚጀምር ሲሆን፤ አሁን በአጠቃላይ በአገር ደረጃ እየተሠራበት ያለው አሠራር ግን ተሰጥኦን በመፈለግ ማሳደግ ሳይሆን ውድደር ተኮር በሆነ የምልመላ ዘዴ በመጠቀምና በማሰልጠን ነው። ይህ ደግሞ ከሚሰለጥኑት አትሌቶች አንፃር ወደ ውጤት የሚመጡት አትሌቶች ጥቂቶች ብቻ እንዲሆኑ ከማድረጉም ባሻገር ውጤት ላይ ተጽዕኖ እያመጣ ነው።

በሥልጠና በኩል ያለውን ችግር በተመለከተ ደግሞ እንደ ፕረዚዳንቱ ገለፃ፤ ስልጠና አካልን እና አዕምሮን በማዳበር ሰልጣኛች የተሰጣቸውን ተግባር በሚገባ እንዲያከናውኑና የታሰበው ግብ ላይ እንዲደርሱ ለማድረግ ያግዛል። ነገር ግን በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ እየተሰጠ ያለው ስልጠና የታሰበውን ግብ እንዲመታ ታስቦ እየተሠራ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንት ፌዴሬሽኑ ተተኪ አትሌቶችን ለማገኘት አልተቻለውም፡፡

በታዳጊና ወጣቶች ፕሮጀክት ስልጠና ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር የሚያድርጉ ባለድርሻ አካላት አደረጃጃት ተግባርና ኃላፊነት በግልፅ ያልተቀመጠ ሲሆን፤ አትሌቲክስ በህብረተሰቡ ዘንድ እንዲዘወተር እና እንዲስፋፋ ለማድረግ የተቀናጀና ወጥ አሠራር አልተዘረጋም፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ በዕለቱ በቀረበው ወረቀት ላይ እንደገለፀው፤ ፌዴሬሽኑ የብሄራዊ አትሌቶች በየአመቱ ከተለያዩ ሁነቶች፣ ከክልል፣ ከክለብ፣ ከአካዳሚና በግል በመመልመል እየሰጠ ይገኛል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የብሄራዊ ቡድን ቀጣይነት አዋጭ አለመሆኑ በጥናት ታይቷል። ስለጠናውም ለአትሌቶች ተቀባይነት አጥቷል። ከዚህ በፊት የብሄራዊ ቡድን 90 በመቶ ከአዲስ አበባ ብቻ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው የብሄራዊ ቡድን አትሌቶች የክልል አትሌቶች በመሆናቸው ለስልጠና አመች አልሆነም። የአዲስ አበባ ዙሪያ አየርና ትራፊክም ለሥለጠና አስቸጋሪ ሆኗል።

በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ፤ የብሄራዊ ቡድኑ ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዋዠቀ መምጣቱን በመግለፅ፤ በየወሩ ለአትሌቶች የላብ መተኪያ በሚል ፌዴሬሽኑ የሚከፍለው ገንዘብና የአሰልጣኝ ደመወዝና ትጥቅ ወጭ ከውጤት ጋር ሲመዘን አዋጭ አለመሆኑ ታውቋል። በመሆኑም ስልጠናን በአጠቃላይ ወደ ክለብ፣ ማዕከል እና ማናጀሮች ዲሴንትራላይዝድ ማድረግ፤ ፌዴሬሽኑ የክትትል የድጋፍ አግባቡን አጠናክሮ ማስቀጠል የውድድር ሥርዓትና ቀጣይነትን ተከትሎ እንዲሄድ ማድረግ ያስፈልጋል።

 

አብርሃም አባዲ

 

Published in ስፖርት

የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን፤

 

ባሳለፍነው ነሐሴ 26 ቀን 2009.ም በናይጄሪያው ግዙፍ ስታዲየም ኢስታዲዮ አቡጃ በተካሄደው የናይጄሪያ (ንስሮቹ) እና የካሜሮን (የአናብስቶቹ) የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በደጋፊዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ያጣራው ፊፋ ቅጣት በይኖባቸዋል፡፡ 60491 ተመልካቾች በታደመው የሁለቱ ኮከቦች ጨዋታ ናይጄሪያ 40 ስታሸንፍ ለናይጄሪያ ቪክቶር ሞስስ፣ ጆን ኦቢ ሚካኤል፣ ክሊቺ ኢናቾ እና ኢጋሎ ግብ አስቆጣሪዎች ነበሩ፡፡

..2018 በሩሲያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ከአፍሪካ አህጉር ለማለፍ በርካታ ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡ ቡድናቸው እንግዳውን የካሜሮን ብሄራዊ ቡድን እንዲረታ ለማበረታታት ስታዲዬም የተገኙት ማልደው ነበር፡፡ የሚጠበቀው ፍልሚያም የብስራት ፊሽካ ተሰምቶ የአፍሪካ ኃያላን ቡድኖቹ ጨዋታቸውን ጀመሩ፡፡ እንግዳው የካሜሮን ብሄራዊ ቡድን እንደተጠበቀው ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን ሳይችል ቀርቶ ሙሉ የጨዋታ ብልጫ ተወሰደበት፡፡

በተክለ ሰውነት ልቀው የሚታዩት ካሜሮኖች፤ በተጋጣሚያቸው ናይጄሪያ በጨዋታ እንቅስቃሴ፣በሥነ ልቦና፣ በግብም ተበልጠው አመሹ፡፡ ጠንካራው የካሜሮን ብሄራዊ ቡድን የግብ ናዳ ወርዶበት 40 በሆነ ሰፊ ውጤት ተሸነፈ፡፡ በስታዲየሙ የነበሩት ናይጄሪያውያን ደጋፊዎች ቡድናቸው የተጎናጸፈው ጣፋጭ ድል አነሳስቷቸው በካሜሮን ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች ላይ ባልተገባ መልኩ ሲዘባበቱ ታዩ፡፡ ስሜታቸውን መቋቋም ተስኗቸው በካሜሮን ተጫዋቾች ላይ አፀያፊ ስድቦችን እስከመሰንዘር ደረሱ፡፡ የተሸናፊው ቡድን ካሜሮን ደጋፊዎችን ወደ ፀብ እንዲያመሩ እስከማስገደድ የደረሰ ዘለፋና ምልክቶችን ማሳየታቸው በዕለቱ ፊፋን አስቆጥቶታል፡፡ የንስሮቹ ደጋፊዎች ስሜት ገንፍሎ ለተመልካች የማይፈቀድ ቦታ በመግባት ስሜታቸውን ለማንፀባረቅ መሞከራቸው ደግሞ ፊፋ ለቅጣት እንዲጋበዝ አድርጎታል።

የዕለቱን ድርጊት የታዘበው ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) የናይጄሪያውያን ደጋፊዎችን ተግባር ያልተገባ ሲል ኮንኖታል፡፡ ይህንኑ ጉዳይም ለአንድ ወር ሲመረምር ከቆየ በኋላ ናይጄሪያ የነሐሴ 26 ቀኑን ተግባር ዳግም እንዳትደገም የሚያስጠነቅቅ ቅጣት አስተላልፏል፡፡ ፊፋ በናይጄሪያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላይ የ31 ሺ ዶላር ቅጣት ማስተላለፉን ዚስዴይ የተሰኘ ዓለም አቀፍ ድረ ገጽ ዘግቧል፡፡ ቅጣቱ የተላለፈው የንስሮቹ ደጋፊዎች ያሳዩትን ያልተገባ ሥነ ምግባር ምክንያት በማድረግ መሆኑን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

ናይጄሪያ የስታዲየም ፀጥታን በማወክ ክስ እንደቀረበበት የፊፋን ድረገፅ ዋቢ አድርጌያለው ብሎ እንደፃፈው፤ይሄ ተግባር የዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፊፋ የደህንነት ደንቦች አንቀጽ 65 እና 67 የሚጥስ ሆኖ የሚገኝ ነው።

ፊፋ የናይጄሪያ ደጋፊዎች ለፈፀሙት አጸያፊ ድርጊቱ የሚመጥነውን የ31 ሺ ዶላር ቅጣት ማስተላለፉን የዘገበው ደግሞ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ነው፡፡ የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን እ..አ በ2016 መጋቢት 29 ላይ በአህመድ ቤሎ ስታዲየም ከግብፅ ጋር ባደረው ጨዋታ ላይ ደጋፊው ሮጦ ወደ ስታዲየም በመግባት የፀጥታ ችግር መፍጠሩንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው አስታውሷል፡፡ የናይጄሪያ ደጋፊዎች ከዚህ ዓይነቱ ተደጋጋሚ አጸያፊ ተግባራቸው እንዲታቀቡ የሰሞኑ የፊፋ ቅጣት አስተማሪ መሆኑን አጃንስ ፍራንስ ዘግቧል፡፡

እንደ ናይጄሪያ ሁሉ የተለያዩ አገራት ደጋፊዎችም ሆነ ተጫዋቾች በጨዋታ ወቅት የማይገባ ተግባራትን እንደሚፈፅሙ የጠቆመው አጃንስ ፍራንስ ፤ፊፋም የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ከስህተታቸው እንዲታረሙ እየሰራ መሆኑንም አንስቷል፡፡ በጀርመን የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ላይ ባሳለፍነው ሰኞ የተላለፈውን ቅጣትም ለማሳያነት አቅርቧል፡፡

የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ከቼክ ሪፐብሊክ ጋር ባካሄደው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ 200 የሚሆኑ የጀርመን ደጋፊዎች የናዚን አርማ በመያዝ ስታዲየሙ ውስጥ ታይተዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም ፊፋ በጀርመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላይ የ33 ሺ ዶላር ቅጣት ጥሏል፡፡ እንደ ናይጄሪያ እና ጀርመን ሁሉ ሌሎች በርካታ አገራት ላይ ፊፋ ቅጣት ማስተላለፉን በዘገባው አካቷል፡፡ የአርጀንቲናን የ67 ሺ ዶላር ፣የፓናማን 51 ሺ ዶላር፣ሃንገሪ ጨምሮ ሌሎች በርካታ አገራት የገንዘብና የነጥብ ቅጣትም ፊፋ አስተላልፏል ሲል አጃንስ ፍራንስ አስነብቧል።

 

ዳንኤል ዘነበ

Published in ስፖርት

በኬንያ ተካሂዶ በነበረው የዓለም ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የወንዶች 4 x 400 ሜትር ዱላ ቅብብል የሽልማት ሥነሥርዓት ወቅት ፤

 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኬኒያ ናይሮቢ አዘጋጅነት በተካሄደው 10ኛው የዓለም አቀፍ ታዳጊ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በአልጄሪያ ቴልሚስ አዘጋጅነት በተካሄደው 13 ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተሳታፊ ለነበረው ልዑካን ቡድን ሽልማት አበረከተ።ተሸላሚዎቹ እያንዳንዳቸው ከአምስት ሺ ብር እስከ ሃያ አምስት ሺ ብር የሚደርስ ሽልማት ከኢፌዴሪ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳውና ከሚኒስቴር ዴኤታው ከአቶ ተስፋዬ ይገዙ ተቀብለዋል።

የአትሌቲክስ ቡድኑ ከባድ ፉክክር አድርጎ ጠንካራ ተወዳዳሪነቱን በማሳየቱ አገሪቱ ከሌሎች አገራት የተሻለ ውጤት በማግኘቷ አኩሪ ድል ማስመዝገቧን የጠቆሙት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳው፤ ለተገኘው ውጤትና ለነበረው ተሳትፎ የገንዘብ ሽልማቱ መጠን በቂ ነው ብለን ባናምንም ለሰራችሁት መልካም ስራ እውቅና መስጠት ተገቢ ነው ።በሁለቱ የውድድር መድረኮቹ ላይ በወጣትና ታዳጊ አትሌቶቻችን ያስመዘገቡት በቀጣይ አገሪቱ በታላቅ አለም አቀፍ የውድድር መድረክ ላይ እንደ ትናንቱ አኩሪ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተስፈኛ አትሌቶች እንዳሏትም ለዓለም ያሳዩበት አጋጣሚ ነው ብለዋል።

ለተመዘገበው ውጤት አሰልጣኞች፤ ክለቦችና ሌሎች ባለሙያዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን በእለቱ የጠቆሙት ሚኒስትሩ ውጤቱ የሚያዘናጋ ሳይሆን የተሻለ ስራ ለመስራት የሚያነሳሳ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አገሪቱ በዓለም ትላልቅ የውድድር መድረኮች በአትሌቲክሱ የተሻለ ውጤትና ስም አትርፋለች። እንደ አትሌቲክሱ ሁሉ በሁሉም የስፖርት መስክ የአገሪቱን ስም በኩራትና በውጤታማነት ለማስጠራት ጥረት እየተደረገ ይገኛል።ይሁን እንጂ ከአትሌቲክሱ ውጭ ባሉ ስፖርቶች የምንመኘውን ውጤት ማግኘት አልተቻለም።በአትሌቲክሱም ስፖርትም ቢሆን አሁን እየመጣ ያለው ውጤት በአገሪቱ ካለው አቅምና ታሪክ ደረጃ ከመዘነው በቂ አይደለም። አገራችንን ወክለው በአህጉራዊና በዓለም አቀፋዊ የውድድር መድረኮች ላይ በመሳተፍ ውጤት ማምጣት የሚችሉ አትሌቶችና ስፖርተኞችን በመመልመልና በማፍራት ረገድ አሁንም ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዓለም አቀፍ ታዳጊ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በአልጄሪያ የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በመሳተፍ በሁለቱም ውድድሮች ላይ ወርቅ በማምጣት ተሸላሚ የሆነው አትሌት ሰለሞን ባረጋ በሽልማቱ እንደተደሰተ ተናግሯል። ‹‹በዓለም ሻምፒዮና እና ኦሎምፒክ ላይ በመሳተፍ ወርቅ በማግኘት ለአገሬ ታሪክ መስራት ነው ህልሜ። ያለኝን አቅምና ብቃት በማጎልበት አሳካዋለው›› የሚል ትልቅ እምነት አለኝ ብሏል።

በአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮን ላይ ተሳታፊ በመሆን የነሃስ ሜዳሊያ በማስመዝገቧ የአስር ሺ ብር ሽልማት የተበረከተላት ቃልኪዳን ንጉሴ በበኩሏ፤ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ የተበረከተልን ሽልማት በስፖርቱ ጠንክረን እንድንሰራ የሚያበረታታን ነው።መንግስት በምናደርገው ጥረት ውስጥ ከጎናችን ሆኖ እንደሚደግፈንም የሚያረጋግጥ ነው ብላለች።

በዓለም ታዳጊዎች ሻምፒዮና ላይ በመሳተፍ የነሃስ ሜዳሊያ ያመጣችው ይታይሽ መኮንን በተመሳሳይ ሽልማቱ የፈጠረባትን መልካም ስሜት በመግለፅ፤ከውድድሩ መልካም ተሞክሮና ልምድ አግንቼበታለሁ።ለአገሬ ወርቅ ማምጣት ባልችልም እንኳን በቀጣይ ጠንክሬ በመስራት እንደነ ጥሩነሽና መሰረት ደፋር አገሬን በትላልቅ የውድድር መድረኮች አስጠራለሁ የሚል እምነት አለኝ።ለዚህም ጠንክሬ እሰራለሁ ብላለች።

ፌዴሬሽኑ ከጎናችን በመሆን የማበረታቻ ሽልማት መስጠቱ ነገ የተሻለ ውጤት እንድናመጣ የሚያበረታታን ነው የሚለው ደግሞ፤በኬኒያ ናይሮቢ በተካሄደው ውድድር ላይ በስምንት መቶ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣው መለሰ ንብረት ነው።የተበረከተለት የ25 ሺ ብር ሽልማት ለተሻለ ውጤት የሚያነሳሳው እንደሆነና፤እርሱም እንደሌሎቹ አትሌቶች ሁሉ አሁን ያለውን አቅምና ችሎታ በማዳበር እንደቀደምቶቹ ጀግኖች አትሌቶቻችን በዓለም ትላልቅ መድረኮች ድል በማድረግ የአገሩን ባንዲራ ከፍ የማድረግ ራዕይን ሰንቆ እየሰራ እንደሆነ ነው የተናገረው።

የሽልማቱ አካል በሆነውና በአልጄሪያ ትለምሰን በተካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳተፈው ብሄራዊ ቡድኑ በ13 የወርቅ፣ 13 የብር እና 12 የነሐስ ሜዳልያዎችን አስመዝግ ቧል። ኢትዮጵያ በድምሩም 38 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የቅርብ ተፎካካሪ የሆነችውን ደቡብ አፍሪካን በማስከተል የአንደኛነትን ደረጃ ይዛ ነው ያጠናቀቀችው።በኬኒያ አዘጋጅነት በተካሄደው የታዳጊ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በውድድሩ 23 አትሌችን በተለያዩ ርቀቶች በማሳተፍ 12 ሜዳሊያዎች አግኝታለች። ከተሰበሰበው አጠቃላይ ሜዳሊያ ውስጥ 4 የወርቅ፣ 3 የብርና 5 የነሃስ ሜዳሊያዎች ናቸው።በዚህም ውጤት መሰረት አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቋ ይታወሳል።

 

ዳንኤል ዘነበ

 

 

Published in ስፖርት
Wednesday, 04 October 2017 18:29

የሳምንቱ ፎቶ

የህንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ሲሪያን ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ባስሊዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ሁለተኛ፣ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፤ ሃይማኖቶች እና መንግስት የተለያዩ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በሀገር ሰላምና ልማት ዙሪያ በጋራ መስራት እንዳለባቸው በብሄራዊ ቤተመንግስት በነበራቸው ቆይታ መክረዋል፤ አስገንዝበዋል።

 

ገባቦ ገብሬ

 

 

 

Published in መዝናኛ
Wednesday, 04 October 2017 18:26

ጊዜና አጋጣሚ

 

ብዘዎቻችን የቡሄ ጅራፍ ከጮኸ በኋላ ክረምት ይሉት ነገር አልያም ጠብታ ያህል ዝናብ እንደሌለ እንገምት ይሆናል። ይህን ወቅት ተከትሎም ጭጋጉ ተገፎ፣ ብራ ጊዜ እንደሚመጣ የምናስብ ጥቂቶች አይደለንም። የዛሬን አያድርገውና ድሮማ «ዶሮ ከጮኸ ሌሊት፤ ጅራፍ ከጮኸ ክረምት አይታሰብም” ይባል ነበር። ዳሩ በድሮ በሬ ማን አረሰና! ድሮ እኮ ያው ድሮ ቀርቷል።

ወይጉድ! እናንተዬ አሁንማ የዘንድሮ ዝናብ የተሰጠውን ገደብ አልፎ መስከረምን ጭምር መጋፋቱን ይዟል። ለእሱ የክረምቱ ጊዜ ብቻ የበቃው አይመ ስልም። ውሎውን በስስ የጸሀይ ብርሀን ብልጭ፣ ድርግም ሲል የሚያረፍደው ቀን ለደንቡ እውነተኛውን መስከረም መስሎ ይታይና ቆየት ብሎ በዶፍና በጎርፍ ያጥለቀልቃል። በተለይ በዚህ መስከረም ወር የታየው ከባድ ዝናብና አስከትሎት የሚደርሰው አስደንጋጭ ጎርፍ የመንገድ ዳር ቤቶችን በስጋት እያንቀጠቀጣቸው ይገኛል።

ክረምቱን ሙሉ በዝናብና በከፍተኛ እርጥበት ሲርስ የከረመው መሬት ጥቂት ካፊያ ሲያርፍበት እንደበጋው ድርቀቱ አይደለም። አሁን ውሀ ብርቁ አይሆንበትም። እንደ ነገሩ ጥቂቱን ተጎንጭቶ በርከት የሚለውን ስለሚተፋም አገር ምድሩን በጎርፍ ማጥለቅለቁ አይቀሬ ነው። ይህ ሲሆን ታዲያ እግረኛ መሆን «ለምኔ» ያሰኛል። ለነገሩ በዚሁ ክስተት እግረኞች ብቻ ሳይሆኑ መኪኖችም ጭምር በድንገቴው ደራሽ ተጥለቅልቀው ሲጨናነቁ እያየነው አይደል?

በተቃራኒው ይህ አጋጣሚ መልካም የሆነላቸው አንዳንዶች ታዲያ የመስከረምን ጸሀይና የዕለቱን ብራነት በእጅጉ ይጠሉታል።ለእነሱ የወቅቱ ዝናብ ማለት የገንዘብ ምንጫቸው ነው። የዕለት እንጀራቸውም ጭምር።እናም ሁሌ ሰማይ ሰማዩን እያዩ ዳመናውን ይናፍቃሉ። የነጎድጓዱን ድምጽም የተወዳጅ ሙዚቃን ያህል ይማረኩበታል። እንደመልካም ገበሬ የሰማዩን በረከት እያንገጠጡም የጠብታን እርጥበት ለማግኘት ይጠባ በቃሉ።

እንደ ዕድል ብሎ ቀኑ ጸሀይ ውሎ ካመሸ እነሱን በእጅጉ ይከፋቸዋል።በለስ ቀንቷቸው ዝናብ መጣል ከጀመረ ግን ደስታቸው በፍጥነት ይመለሳል።ይህ አጋጣሚ ማለት ለእነሱ መልካም የሚባል ነው።የዛኔ ትከሻቸውን አስፍተውና ክንዳቸውን አፈርጥመው ወጪ ወራጁን ይጠብቃሉ።ዝናቡ በቶሎ ዘንቦ እንዳያባራም ለምኞታቸው ደግመው ደጋግመው ይጸልያሉ።

በአፍታ ቆይታ ጎዳናው በድንገቴው ጎርፍ ሲጥለቀለቅ የእነሱም ጸዳል በደስታ ብርሀን ይፈካል።እናም ስራቸውን ለመጀመር የልብሳቸውን እጅጌ ሽቅብ ይሰበስባሉ፣ ሱሪያቸውን እስከ ጉልበታቸው ጠቅልለውም በእጆቻቸው ላይ የሚያርፉ መንገደኞችን ለማደን አይኖቻቸው ከላይ ታች ይባዝናሉ።የዛኔ ምርጫ የሌላቸው ሰዎች ይቀርቧቸዋል።

እርስዎ የዛን ዕለት ከቤትዎ ወጥተው ወደቤትዎ ሳይመለሱ ዝናቡ ከደረሰብዎና እግረኛ ከሆኑ በነዚህ ሰዎች ፈርጣማ ክንዶች ላይ ለማረፍ ሊገደዱ ይችላሉ። በነገራችን ላይ እነዚህ የምላችሁ ሰዎች ዝናቡን ጠብቀው ኪስ የሚያወልቁ፣ አልያም የመንገዱን በጎርፍ መጥለቅለቅ ተጠቅመው ማጅራት የሚመቱ ዘራፊዎች እንዳይ መስለችሁ። ዝናብና ጎርፍ ናፋቂዎቹ ፈርጣሞች ወንዝ አሻጋሪዎች ናቸው።በጉልበታቸው ተማምነውና አጋጣሚውን በወጉ ተጠቅመው ድንገቴውን የከተማ መሀል ጎርፍ በስልት የሚያሻግሩ ባህረኞች።

እነሱ ዘንድ የመሻገሪያው ምርጫ ሰፊ ነው። ቢሻዎት በሸክም፣ አልያም በእነሱ ድጋፍ ተመርኩዘው የማለፍ መብት ይሰጥዎታል።ታዲያ እርስዎ ለዚህ አገልግ ሎታቸው የተጠየቁትን ገንዘብ ቅድሚያ እጃቸው ላይ ማኖር ይጠበቅብዎታል።ይህን ለማድረግ አቅምዎ ባይፈቅድና ባይፈልጉ ግን ድንገቴው ጎርፍ ተጠራርጎ የቀድሞው ውሀ አልባ መንገድ ቁልጭ ብሎ እስኪታይ ለሰአታት ምንአልባትም እስከምሽት ድረስ ቆመው ለመጠበቅ ይገደዳሉ።

አንዳንዴ ታዲያ መንገድ በመምራት የሚያሳልፉት እነዚህ ሰዎች ለሸክም ከበድ ያለ ሰው ሲገጥማቸውና ተሻጋሪው ከሁለት በላይ በሆኑ ሰዎች ለመደገፍ ፍላጎት ሲያሳይ የሚያስከፍሉት ገንዘብ ከመደበኛው በእጥፍ ሊጨምር ይችላል።ግለሰቡ በአስተማማኝ እጆች ላይ ማረፉ እንዲሰማውም የተለየ እንክብካቤና ጥንቃቄ ይደረግለታል።እነሱ ጉልበታቸውን እርስዎም ገንዘብዎን ይጭነቀው እንጂ እንደልጅነትዎ በሸክም፣ አልያም በእዝል ሆነው መንገዱን መሻገር ይችላሉ።

ዕድሜ ለአስፓልት መንገዶቻችን ሽንቁሮች ይሁንና ጥቂት ጠብ ሲል ፈጥኖ ሆድ የሚብሰው ጎዳና ለብዘዎች የገቢ ምንጭ መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል።ሆኖም ግን እንደ ዘንድሮ ክረምት በተለይ ደግሞ እንደ መስከረም ወር አስገራሚ የሆነበት ጊዜ የለም ለማለት ያስደፍራል። ይህ አጋጣሚ ተደጋግሞ በሚስተዋልበት የመካኒሳ ጀሞ ጎዳና ተግባሩን ስራዬ ብለው የያዙ ወጣቶች አንድም ለኪሳቸው ሌላም ደግሞ ግራ ለገባቸው እግረኞች መፍትሄ ሲሆኑ ቆይተዋል።

እንግዲህ ጊዜና አጋጣሚዎች ምን እንደሚያስከትሉ አይታወቅም። ብዙዎቻችን ክረምቱ አልፎ መስከረም እንደጠባ እናውቃለን።ወቅቱን ጠብቀንም ጸሀይና ብራ የሆነ ዘመንን እየናፈቅን ነው።ከዳመናውና ከዝናቡ ጋር የተወዳጁ የሚመስሉ ክረምት ናፋቂዎች ግን ዛሬም ሰማይ ሰማዩን እያዩ ዶፍ ዝናብን ይጠብቃሉ። ዝቅ ብለውም የመሬቱን በጎርፍ መጥለቅለቅ ይቃኛሉ። ቀናቸው ሆኖ ሰማይ ምድሩ ካለቀሰላቸው እሰዬው ነው። እንደተለመደው የሚታዘለውን አዝለው፣ የሚታ ቀፈውንም ታቅፈው ኪሳቸውን ይሞላሉ። ምንአልባት ግን መስከረም የቀድሞ ማንነቱ ትውስ ብሎት በከረረ ጸሀይ ውሎ ምሽቱንም ከጨከነባቸው ሲደብራቸው ውሎ ያድራል።

አንዳንዴ አጋጣሚዎች ሌሎች አጋጣሚዎችን አስከትለው ሲመጡ ማስገረማቸው አይቀርም። «ግርግር ለሌባ ያመቻል» እንዲሉም ብዙ ግዜ በሚከሰቱ አጋጣሚዎች መሀል ሌሎች ትናንሽ ክስተቶች ይፈጠሩና ለብዙዎች ጉዳት አልያም ጠቀሜታን ሲያስገኙ ይስ ተዋላል። ይህ ሲሆን ደግሞ የተጠቀመው ሲደሰት አጋጣሚው ያልበጀው ደግሞ ይከፋል ወይም ያማርራል።

ወዳጆቼ! አሁን እኮ ጊዜው እንደሰዎች አመል እየተቀያየረ ነው። በየወቅቱ ስማቸውን አሳምረው «አለን» የሚሉት እነ ኤሊኖ፣ ካትሪና፣ ሄሪኬንም ክረምትና በጋውን በወጉ እንዳንለየው ሳያደርጉን አልቀሩም። የዚህ ክስተት ቀን መቁጠሪያው በእጃቸው ያለ የሚመስለው የኛዎቹ ወንዝ አሻጋሪዎችም ጊዜው እንደታሰበው እንደማይዘልቅ ጠንቅቀው አውቀውታል። ዛሬም በወርሀ መስከረም ፍንትው ባለችው ጸሀይ ስር ዳመናውን ይፈልጋሉ። አናት በሚበሳው ሙቀት መሀልም ዶፍ ዝናብን ይናፍቃሉ።

መቼም ማንም በሰራው ልክ ቢያገኝ የሚፈረድበት አይሆንም።የጊዜውና የአጋጣሚዎች መገጣጠም ግን መተዛዘን ይሉትን መልካም ባህል ጨርሶ እንዳያጠፋው ደግሞ መጠርጠሩ አይከፋም።አንዳንዴም ደግሞ ለራስ ህሊና ማደሩ መልካም ነው።ትንሽ ስራን ከውኖ ከሚገኝ ሽርፍራፊ ጥቅም ይልቅም«ተባረክ፤ እደግ ተመንደግ »ይሉት ምርቃት እንደሚበልጥ ማወቅም ይበጅ ነበር።

ወዳጆቼ!እንዳልኳችሁ መስከረምን ልናጠናቅቅው ተዳርሰናል።አሁንም ግን ሰማዩ እያጉረመረመ በዝናቡ ማስፈራራቱን ቀጥሏል።ወይ ጉድ! ደግሞ ዛሬ የትኛው ሰፈር ተጥለቅልቆ ይሆን?ለማንኛውም በሽንቁሩ የአስፓልት ጎዳና የምታልፉ መንገደኞች፤በጊዜ ቤታችሁ ገብቶ ለማደር የኪሳችሁን አቅም ፈትሹ።አለበለዚያ ቀናችሁ መምሸቱ አይቀሬ ይሆናል።«ልጄ፣ እስቲ አሻግረኝ፣አሳልፈኝ፣ብሎ እጅን መስደዱና ምርቃትን ማዥጎድጎዱ የሚያዋጣ ሆኖ አልተገኘም።ዛሬ ሁሉ ነገር በገንዘብ ሆኗል።«በኮይን» ነው የሚሉት አራዶቹ።አዎ!በኮይንና በኮይን ብቻ። ወይ ጊዜና አጋጣሚ።

 

መልካምስራ አፈወርቅ

Published in መዝናኛ

 

ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት አማራጮች መካከል የታክሲ ትራንስፖርት አንዱ ነው። ከዚህ አገልግሎት ጀርባ ያለውን ተግባር በማቀላጠፍ የታክሲ ረዳቶች ሚና የላቀ ነው። የማለዳውን ቁር፣ የቀትሩን ፀሐይ የምሽቱን ብርድ በመቻል ተጠቃሚውን ለማገልገል መስዋዕትነቱን ይከፍላሉ። በመዲናዪቱ ሕይወታቸውን ይለውጡበታል። ልበ ቢሶች ደግሞ በዚሁ ሙያ ውስጥ ለውጥን ሳያዩ ይራመዳሉ። የአዲስ ዘመኑ ዳንኤል ዘነበ ይሄንኑ በታክሲ ረዳትነት ሙያ ውስጥ ያሉና በተለያየ የሕይወት አቅጣጫዎች የተጓዙ የታክሲ ረዳቶችን ተሞክሮ በመቃኘት እንዲህ አቅርቦታል።

 

ከማለዳ ጀምሮ የታክሲ ረዳቶች ድምፅ በመዲናይቱ አዲስ አበባ አራቱም አቅጣጫዎች ዘወትር ይሰማል። ከዚህ ድምፅ ጀርባ ከሚገኙት በርካቶቹ ውስጥ ክብሮም መስፍን እና የጌታቸው ረጋሳ አካል ይገኙበታል፡፡ ሁለቱ ወጣቶች የተግባራቸውን ምዕራፍ ለመጀመር በጋራ ከሚኖሩባት አነስተኛ ቤታቸው ማልደው ይነሳሉ። ከሚኖሩበት ጨርቆስ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢም ወደ ሜክሲኮ ያቀናሉ። የረዳትን ስራቸውን ለማከናወን አመሻሽተው ወደ ቤታቸው መግባታቸው፤ማልደው በመነሳት ስራቸውን ለመጀመር ሳያግዳቸው ዳግም ማልደው ከቤታቸው ይወጣሉ።

የጋራ ጎጆንና የጋራ ሙያ ያላቸው ጌታቸውና ክብሮም፤ የትናንት የህይወት ልምዳቸው፣ አስተዳደጋቸው ሌሎች ሁኔታዎች እንደ ስራቸው አቅጣጫ ሁሉ ተቃርኖ የነበረው ነው። ነገር ግን የህይወት አጋጣሚ ከአንድ ቤት ውስጥ፣ ከአንድ አይነት ሙያ አብሮ ያኖራቸዋል። ሻሸመኔ ከተማ ትውልድና እድገቱ የሆነው ጌታቸው የኑሮውን አሃዱ የጀመረው በዚሁ ትውልድ መንደሩ ነው። እስከ አስረኛ ክፍል የነበረውን ትምህርቱን በማጠናቀቅ አዲስ አበባ ከትሟል። በትውልድ መንደሩ ከቤተሰቦቹ ጋር ከችግር የራቀ ኑሮን አሳልፏል። ከወላጆቹ ጋር ወፍራም እንጀራ በመብላት እድሜውን ገፍቷል። የአስረኛ ክፍል ትምህርቱን ውጤት ወደ ፊት የሚያራምድ አለመሆኑ ደግሞ በወጣቱ የወደፊት ጉዞ ላይ ትልቅ ጥላን አጠላበት። ከትምህርት ውጪ ሌላ ምዕራፍ እንዳያይ ተደርጎ ያደገው ይህ ወጣት፤ የያዘው መንገድ ሳይሳካ በመቅረቱ ምን ማድረግ እንዳለበት አላወቀም። ትምህርቱንም አጠናቆ ያለ ስራ ሁለት ዓመታትን ተራመደ። ያለ ስራ ህይወትን መግፋቱ ዳገት ሆኖበት። በአንድ የስሜት ግፊት አዲስ አበባ ላይ ተገኘ። ለምንና ምን መስራት እንኳን ሳያውቀው ያለ እቅዱ የተገኘባት ከተማ የቤተሰቦቹን እጅ ያህል አቅፋ አልተቀበለችውም፡፡ የወጣቱ እጣ ፋንታውም ጎዳና ላይ ሆነ።

የጎዳና ህይወትን ለመቋቋም ትግሉን ይጀምራል። ያልለመደውና የማያውቀው የሱስ ህይወት ውስጥ ሳይወድ በግዱ ይገባል። ህይወት በተቃራኒ መንገድ መርታም ከአንድ ጫት ቤት አስቃሚ ሰው እጅ ላይ ጥላዋለች። የሱስ ተገዥ በመሆኑም ለሰውዬው የእለት እንጀራዬን ስጠኝ ሳይሆን፤ የእለት ሱሴን ሙላልኝ አይነት ኑሮን መግፋት ጀመረ፡፡

ግራ በገባው ህይወት ውስጥ የተገኘው ጌታቸው፤ በመላላክ በሚያገለግልበት ቤት ውስጥ ደንበኛ የሆነውን ክብሮም ተዋወቀ፡፡ ከዚህ ህይወት ውጣ ሰርተህ ተለወጥ በሚል እርሱ የሚሰራውን የታክሲ ረዳትነት ስራ እንዲሰራም ምክሩን ለጌተቻው ያቀርብለታል። ከምክር በመዝለልም እርሱ ከሚያውቃቸው ባለ ታክሲዎች ከአንዱ ጋር በማገናኘት ስራ እንዲጀምር ያደርገዋል።

የክብሮም እዝነት በዚህ አላበቃም፡፡ ስራውን ብቻም ሳይሆን እርሱ ከሚኖርባት አንድ ክፍል ቤት አብሮት መኖር እንዲሚችል ፍቃዱን ይጠይቀዋል። መድረሻ ያጣው ጌታቸው ይሄንኑ የክብሮምን እርዳታ ቸል ባለማለት ተቀብሎ ህይወትን እንደ አዲስ ማጣጣም ይጀምራል። ከነበረበት የጭለማ ኑሮው በመውጣት ስራውን አሃዱ ብሎ ይጀምራል። የራቀው ተስፋው ዳግም ቀርቦታል። የሁለቱ ጥምረት መልካም ባይመስልም የህይወት መስመሩ ውጥንቅጡ ለወጣበት ጌታቸው ግን አዲስ ወድቆ መነሳት ሆነለት፡፡

በታክሲ ረዳትነት ህይወት ውስጥ ያለውን ውጣ ውረድ አብረው ተሸክመው በአንድ ጥላ ስር መኖር ቀጠሉ። ጌታቸው ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ በሚዘልቀው መስመር ሲሰራ ይውላል። ክብሮም በፊናው ከሜክሲኮ ፒያሳ የአገልግሎቱን ጥሪ ያሰማል። ተሳፋሪው ወርዶ አቅጣጫውን ሲቀጥል፤ እነርሱ ሌላ ጩኸት ያሰማሉ፤ ተረኛውን ተጓዥ ይጭናሉ፤ ያወርዳሉ። የጠዋቱ ቁር፣የከሰዓቱ ፀሃይ፣ የምሽቱ ብርድ ይፈራረቁባቸዋል። የዚህን አስቸጋሪ የስራ ሂደት የገባውና ተረድቶ የሚያዝን ተሳፋሪ ግን ጥቂት ነው። የሚሰጣቸው ክብርና ቦታ ከተግባሩ ያፈነገጠ ነው።ወጣቶቹ ረዳቶች የአስራ ሁለት ሰዎችን ባህሪ መጋፈጥ ግድ ይሆንባቸዋል። ጉዞው ግን በፈተናዎች ሳይታጀብ የመሄዱ ነገር የማይታሰብ ነው።

በተለይም ክብሮም በረዳትነት አራት ዓመታትን እንደመሻገሩ ሁኔታዎች አበጥሮ ያውቃቸዋል። እነዚህን ፈተናዎች ከመሳደብ እስከ መደባደብም በመድረስ ያልፋቸዋል። ወደ ታክሲው የገባው ተሳፋሪ ምናልባትም የመውረጃው ፌርማታ ጋር ደርሶ እስኪወርድ መልስ ስጠኝ አትስጠኝ የሚገጥመው ሙግት እስከ ዱላ ቀረሽ ስድብ ድረስ የተጓዘበት አጋጣሚ ለቁጥር የሚከብደው ነው። ማልዶ በሚጀመረው የክብሮም የረዳትነት ተግባር ውስጥ እነዚህ ፈተናዎች በመጋፈጥ፤አመሻሽ ላይ ይጠናቀቃል። ከሜክሲኮ የሚነሳው የአገልግሎት ጥሪ ምሽቱ ሲመጣ ዞሮ ሜክሲኮ ላይ ይገታል። ማለዳ ከተነጠለው ጌታቸው ጋር ተያይዘው ወደ ጋራ ቤታቸው ይከተታሉ። ማልደው ለመነሳት ቀጠሮ ይይዛሉ። በስራው የሚያጋጥማቸውን ፈተናዎች በማለፍ ረገድ ሁለቱም በተለያየ መንገድ ይጓዛሉ።

የብዙ ሰዎችን ባህሪና፤ሰብእናን የጎደለው ድርጊት በመጋፈጥ ተግባሩን ሲያከናውን የኖረው ክብሮም፤ ከአንዳንድ ተሳፋሪዎች ያልተገባ ድርጊት በሚንፀባረቅበት ግዜ ዱላ እስከ መሰናዘር የደረሰ እርምጃን ሊጓዝ ይችላል። እንዲህ አይነት ሁኔታዎችን በትግስት ለማሳለፍ ላለመፈለጉ ደግሞ የራሱ ምክንያት አለው። እርሱም ሆነ እንደ እርሱ በሙያው ውስጥ የሚገኙ ረዳቶች ከተሳፋሪዎች ጋር ለሚያሳዩት ያልተገባ ድርጊት ዋናው ምክንያትነት እነሱን ዱርዬ አድርገው መቁጠራቸው ነው፡፡ “ብዙ ተሳፋሪዎች የታክሲ ረዳት ሲባል እንደ ዱርዬ፣ ተስፋ ቢስ፣ለሰዎች እዝነት የማያውቅ አድርገው ይወስዳሉ። ይሄን አይነት አመለካከት በተሳፋሪዎች አዕምሮ ያለ በመሆኑ ረዳቱ ቢሳሳትም ባይሳሳትም ተሳፋሪው ይሳደባል፡፡ ይሄ ሁኔታም እኔንም ሆነ ሌሎች ረዳቶችን ያበሳጫል፡፡ ስለዚህ ለጠብ እንዳረጋለን” ሲል ነው ክብሮም የሚናገረው፡፡

በእነዚህና መሰል የፈተና ሁኔታዎች ገፈት ቀማሽ በመሆን የተሻገረው ክብሮም፤ የእነዚህ አተያይ ድምር ነገውን እንዳያማትር ያደረጉት ይመስላል። ክብሮም የታክሲ ረዳትነት ስራን ባለፉት አራት ዓመታት ተፈትኖ አልፎበታል። የሙያ ፈተናዎች ግን ያልተገባ ማንነት አላብሰውታል። የአንድ አንድ ድምፃውያን የተጣመመ የዜማ ምክር በውስጡ የሰረፀም ይመስል፤ የዛሬን መኖርን ብቻ ነው የሚያስበው። “ዛሬ ልሙት ነገ አላውቅም፡፡ ለምንድነው የምጨነቀው፤ሺ አመት አልኖር፡፡ አትጨናነቅ አትጨናነቅ ” ሲልም ነው የነገ ዓላማ እንደሌለው የሚገልጸው፡፡

የጌታቸውን የእለት ውሎ ከዚሁ እውነት የፀዳ ባይሆንም ቅሉ አፀፋው ግን የሚለያይ ነው። ወጣት ጌታቸው ምንም እንኳን በባህሪው ዝምታን የሚያበዛ አይነትና የመልካም ሰብእና ባለቤት አይነት ሰው ቢሆንም ከዚህ ችግርና ገጠመኝ ግን ሰለባ ከመሆን አልተረፈም። የቱንም ያህል ጥሩ ሰብዕና ቢኖርህም ከግጭት ውጪ መሆን አትችልም ሲል ነው የሚናገረው። ገና ታክሲ ውስጥ ዘው ከማለቱ በሹፌሩ ላይ ሳይቀር ዘለፋ የሚያወርድ ተሳፋሪ ብዙ ነው፡፡ ይሄንኑ ሁኔታ በመቻል የእለት እንጀራውን ለመጋገር ከመታተር ግን ቦዝኖ አያውቅም። ጌታቸው የሰዓት ገደብ በሌለው በዚህ ስራው በቀን እስ 200 ብር ገቢ ያገኛል። አንዳንዴ ደግሞ እስከ 300 ሊዘልቅ ይችላል። ይሄው ገቢ የስራው አድካሚነትን፤ ከተሳፋሪ ጋር ያለውን ግጭት ያስረሳዋል።ወደ ስራው ያሳለፈውን አንድ ያህል ዓመት ራሱንም ሆነ ቤተሰቦቹን ለመደጎም አስችሎታል።

በሚያገኘው ገቢ መሰረት በማድረግም በቀን የመቶ ብር እቁብ ይጥላል። ይሄም በድካም የሚያገኘውን ገንዘብ ባልተገባ መልኩ እንዳይበትን አስችሎታል። ከረዳትነት ወደ ሹፌርነት ለመሸጋገር የሚያስቸለውን የመንጃ ፍቃድ ትምህርቱን ወጪ ያለ ሃሳብ ለመሸፈን ይሄው እቁብ መከታ ሆኖለታል። ወጣት ጌታቸው የነገውን ማንነቱን ገንብቶ እስኪያጠናቅቅ የስራውን ውጣ ውረድ በመቋ ቋም ማከናወኑን ቀጥሏል። ይቀጥላልም። ዛሬ ከክብር ጥግ መጣሉ፤ለነገ ማንነቴ እችለዋለሁ ሲል ያስባል። ይህ እስኪሆን ግን ከማለዳ እስከ አመሻሽ ሲጮህ ይውላል፤ ተሳፋሪ ሲጣራ፡፡

ሁለቱ ወጣቶች የጋራ በሆነችው ቤታቸው፣ በረዳትነት ሙያቸው ዛሬም አብረው ቀጥለዋል። እንደ ተለያየው የስራቸው አቅጣጫ ሁሉ ዛሬ እያራመዱ የሚገኙት የህይወት ፍልስፍናቸውም ነጋቸው የሚለያይ እንደሆነ የሚያሳብቅ ቢሆንም፤ ዛሬን አብረው መጓዛቸውን አልገታውም። ከሚኒባሱ በር ላይ የሚሰማው የአገልግሎት ጥሪያቸውም ከነፈተናው ቀጥሏል፤ ወደፊት ይጓዛል።

 

ዳንኤል ዘነበ

Published in ማህበራዊ

 

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ ፤                                           አቶ ካህሳይ ገብረእየሱስ ፤

 

በኦሮሚያ እና በኢትዮ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተነሳው ግጭት እስካሁን ትክክለኛው ቁጥር ይፋ ባይሆንም የሰዎች ህይወት አልፏል። ዜጎች ከሚኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለዋል። አሁን አሁን በተለያዩ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ግጭቶች እየተከሰቱ ነው፡፡ በተለይ በኢትዮ ሶማሌ ክልልና በኦሮሚያ፤ በአፋርና በኢትዮ ሶማሌ አርብቶ አደሮች አካባቢ በግጦሽ መሬት፤ በውሃ ፍለጋና ከብት በመሰራረቅ ምክንያት ግጭቶች ይከሰታሉ።

እነዚህ ግጭቶች እንደተጠቀሰው ከግጦሽ መሬትና ውሃ ጋር በተያያዘ የሚነሱ እንጂ ብሔር ላይ ያተኮሩ አልነበሩም የሚሉት የአፍሪካ ሂውማኒተሪያን አክሽን ምክትል ፕሬዚዳንትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ የሚከሰቱት ግጭቶች ግን እንደቀደመው ጊዜ በጦርና በቀስት ከመጣላት አልፎ ዘመናዊ መሳሪዎችን በመጠቀም ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው ይላሉ፡፡

‹‹በአንዲት ሉዓላዊት አገር ላይ በዜጎች መካከል የእዚህ አይነት ግጭቶች መካሄድ የለባቸውም፡፡ የሁለቱ ክልል መንግሥታት ግጭቱን ማብረድና ሁለተኛ እንዳይደገም መከላከል ብሎም አጥፊዎቹን መምከርና ወደ ህግ ማቅረብ ሲገባቸው በአንጻሩ ሁለቱ ክልሎች በመገናኛ ብዙኃን ሲወነጃጀሉ ይሰማል፡፡ ይህ አግባብ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በህዝብ ተመርጠው ህዝብን የሚያስተዳድሩ የመንግሥት አካላት የአንድ ሰው ህይወት እንዳይጠፋ መሥራት አለባቸው እንጂ በመገናኛ ብዙኃን ንትርክ ውስጥ መግባት የለባቸውም፡፡ ስለዚህ የመንግሥት አካላት ለግጭቶች ዘላቂ መፍትሄ በመስጠት ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊኖራቸው ይገባል›› ነው ያሉት፡፡

እናም ይላሉ ዶክተሩ ተመሳሳይ ግጭቶች እንዳይፈጠሩና እንዳይስፋፉ ከወዲሁ ባለሙያዎች፣ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች የተሳተፉበት ምክክር ተደርጎና ህዝቡንም አነጋግሮ በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበት መላ በመዘየድ ረገድ ከፍተኛ ስራ መስራት አለበት፡፡ ግጭቶች በሚነሱበት ጊዜ የአካባቢው አስተዳደር ብሎም ክልሎችና የፌዴራል መንግሥቱ ፈጥነው መፍታት አለባቸው፡፡ እንዲሁም በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን የሚያስጠብቁ ህግ አስፈጻሚ አካላት ግጭቶቹ የቆዩ ከሆኑና ችግሮቹ በየጊዜው የሚነሱ ከሆነ የችግሮቹን ምንጭ ለማድረቅ ከፍተኛ ስራ መስራት ይኖርባ ቸዋል፡፡

መንግሥት ሁሉንም ዜጎች ከጥቃት መከላከል ቢኖርበትም እርምጃዎችን የሚወስደው ግን ጉዳዩን አጢኖ መሆኑ ተገቢ ነው፡፡ በቀጣይ ግን ፈጥኖ መልስ መስጠት የሚቻለው ግጭቶች ሊነሱ ይችላሉ በሚል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ዝግጅት ሲደረግ ነው፡፡ ግጭቶች እንዳይከሰቱ ጥናት እያጠና ለመንግሥት ምክረ ሀሳብ የሚያቀርብ ገለልተኛ ተቋም መቋቋም ይኖርበታል፡፡ የተቋሙ ተግባርም የግጭቶች መነሻ ምንድነው? ወደፊት እንዳይከሰቱ ምን ማድረግ አለበት? ቢከሰትስ ፈጥኖ ምን መደረግ ይኖርበታል? በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ ጥናት እያጠና ለመንግሥት ምክረ ሀሳብ ማቅረብ ይሆናል ሲሉ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡

በአጭር ጊዜ በግጭቱ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቤተሰቦች የሚካሱበትን መንገድ ክልሎች ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ‹‹ማንም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ክልል ሄዶ መኖር የሚችልበትን መንገድ እንዲፈጠር ከትም ህርት ቤት ጀምሮ ስለ ብቁ ዜግነት፣ ዜጎች ለአገራቸው ስለሚኖራቸው ፍቅርና ቁርጠኝነት ዙሪያ ከፍተኛ የትምህርት ስራ የሚያስፈልግ ይሆናል፡፡ ህዝቡንም በተለያዩ መድረኮች በእድርም፣ በህዝባዊ ማህበራት ስለ አብሮ መኖር ዙሪያ ጥልቀት ያላቸው ትምህርቶች መስጠት ይገባል እንጂ አንተ የእዚህ ጎሳ ሰው ነህ ቋንቋህ ይኸ ነው፤ አንቺ ደግሞ የእዚህ ጎሳ አባል ነሽ ቋንቋሽ ይህ ነው የሚል ትምህርት የሚሰጥ ከሆነ አገሪቱን ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ብዙ አፍሪካ ውስጥ የምና ያቸው ግጭቶች ከዚህ እንደተነሱ መገንዘብ ያሻል›› ሲሉ ትምህርት ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚገባ ምክረ ሀሳባቸውን ሰዝረዋል፡፡

ግጭቶች የሚከሰቱት በሁለት መንገድ ነው የሚሉት ደግሞ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩና በግጭትና ግጭት አፈታት ዙሪያ የሚሰሩት አቶ ካህሳይ ገብረእየሱስ ናቸው። እርሳቸው እንዳሉትም አንደኛው በሀብት ፍትሀዊ አጠቃቀም ላይ ሲሆን፤ በተለይ በአርብቶ አደሮች አካባቢ ለግጦሽ ሳርና ውሃ ፍለጋ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል ይንቀሳቀሳሉ። በዚህ ጊዜ ግጭት ይነሳል።

ሁለተኛው መንስኤ አካባቢው ያለው ሀብት ያላግባብ መጠቀም የሚፈልጉ ኪራይ ሰብሳቢዎች የፈጠሩት ነው የሚል እምነት አላቸው። ከዚህ አንጻር የሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት ይኸ እንደሚከሰት ያውቃሉ የሚሉት አቶ ካህሳይ ምክንያታቸው ደግሞ ችግሩ የቆየና ተደጋግሞ የሚያጋጥም መሆኑ ነው። ሆኖም በፌዴራል መንግሥትና በሁለቱም ክልሎች በኩል ችግሩን ለመፍታት ጥረት ቢደረግም ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት አልተቻለም ብለዋል።

ህገ መንግሥቱ ለክልሎች የየራሳቸው የስልጣን እርከን ስለሰጣቸው የፌዴራል መንግሥት በእያንዳንዷ በየክልሉ የሚያጋ ጥሙ ችግሮች በቀጥታ ጣልቃ በመግባት ሊፈታ አይችልም። ክልሎቹ በስራቸው በሚገኙ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ችግሮች መፍታት ደግሞ ህገ መንግሥቱ ይፈቅድ ላቸዋል ብቻ ሳይሆን ያስገድዳቸዋል። ነገር ግን ይህን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ እየተሰራ አይደለም ሲሉ ሁለቱንም ወገኖች ተችተዋል።

እንደ አቶ ካህሳይ ገለፃ፤ የወሰን ግጭቶች በራሳቸው በክልሎች የማይፈቱ ካልሆነ ፌዴሬሽን ምክር ቤትና የፌዴ ራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ጉዳዮች አይተው መፍትሄ መስጠት አለባቸው። ነገር ግን ሲፈቱት ወሰኑን ብቻ ሳይሆን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር እንዲሁም የፖለቲካና ህገ መንግሥቱን የማስረፅ ስራዎችንም ጭምር ማካተት ይኖርባቸዋል። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ሁለቱም ተቋማት ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት ሳይሆን ከተፈጠሩ በኋላ እሳት የማጥፋት ስራ ነው እየሰሩ ያሉት።

ግጭቶቹ ደግሞ የፖለቲካ፣ የኢኮ ኖሚ፣ የባህላዊና ማህበራዊ መገለጫ አላቸው። ሁለቱም ተቋማት በጋራ ዕቅድ አውጥተውና ችግሮችን ለመከላከል እየተናበቡ ቀጣይነት ያለው ስራ መስራት ካልቻሉ በስተቀር ችግሩ ሲፈጠር አስታርቆ በመመለስ ጤነኛ የችግሮች አፈታት አካሄድ አይደለም። የችግሮቹ መንስኤ ምንድን ናቸው ተብሎ በቀጣይነት እየተጠና መፍትሄ እየተሰጠው መሄድ ይኖርበታል የሚል እምነት አላቸው።

በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ዘላቂ መፍትሄ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ሲሳይ መለሰ እንደሚሉት፤ በኦሮሚያና በኢትዮ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የተነሳው ግጭት ሁለት መሰረታዊ መነሻ ምክንያቶች አሉት ብለው ለይተዋል፡፡ አንደኛው ድህነትና ኋላቀርነት ሲሆን ሁለተኛው መንስኤ ደግሞ የመልካም አስተዳደር እጦት ነው፡፡ በተለይ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በአገሪቱ እዚህም እዚያ የሚከሰቱት ግጭቶች ለመፈታት መንግሥት በየደረጃው ጥልቅ ታህድሶ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በጥልቅ ተድህሶው እንደ ችግር የተለየውም የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ነው፡፡ ችግሩ ያልተገባ ጥቅም በመፈለግና በመፈጸም እንዲሁም በጠባብነትና በትምክህት ይገለጻል፡፡

ስለዚህ የግጭቶቹ መንስኤዎች መካከል ዋናው መልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት ካለመፍታት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ይህም ህዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ላይ ፈጥኖ ውሳኔ አለመስጠት መሆኑን ያብራራሉ፡፡ ሌላው ከአስተዳደራዊ ወሰን ማካለል ጋር ተያይዞ የመነጨ ነው፡፡ አስተዳደራዊ ወሰን ማለት የሁለት አገራሮች ወሰን ሳይሆን በፌዴራል ስርዓቱ ክልላዊ አወቃቀር ተዋቅሯል፡፡ ይህ ለአስተዳደር አመቺነት ሲባል እንጂ የህዝቦችን ሁለተናዊ አንድነት የሚያናጋ፣ መቀራረብና ተደጋግፎ ማደግን የሚገድብ ወይም አንዱ ክልል ከሌላው ክልል ደሴት ሆኖ ይኖራል ማለት አይደለም፡፡

ሆኖም የጠባብና የትምክህት አስተሳሰቦች አስተዳደራዊ ወሰንን እንደ ምክንያት በመጠቀም በተለያዩ አካባቢዎች ወደ አላስፈላጊ ግጭት የመለጠጥ አዝማሚያዎች ይታያሉ፤ ግጭቶችም ይከሰታሉ፡፡ ስለዚህ ሌሎች አባባሽ ምክንያቶች ቢኖሩም ከመልካም አስተዳደር ጋር የሚያያዘው ችግር ጎልቶ ይታያል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ባለፉት አምስት ዓመታት ብዙ የልማት ስራዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡ ልማትን እያፋጠንንና የመልካም አስተዳደሮች ችግሮች ተለይተው እየተፈቱ በሄዱ ቁጥር ግጭቶች እየቀነሱ ይሄዳሉ የሚል እምነት አለኝ ነው ያሉት፡፡

የግጭቶቹ መንስኤ ፌዴራሊዝም ስርዓቱ ብሔርን መሰረት አድርጎ በመዋቀሩ ነው ብለው የሚሞግቱ ወገኖች ቢኖሩም አቶ ሲሳይ የኢትዮጵያን የኋላ ታሪክ መቃኘት በቂ መልስ ይሰጣል ይላሉ፡፡ "በደርግ ዘመንም ሆነ ቀደም ሲል በነበሩ መንግ ሥታት የማንነት ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ አገራችን ብዙ የእርስ በርስ ግጭቶችን አስተናግዳለች፡፡ የእነዚህ ግጭቶች መነሻ ምክንያት ደግሞ የማንነት ወይም የብሔር ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ነው፡፡ ለእዚህ ጥያቄ ምላሽ በሚሰጥ መልኩ ህገ መንግሥቱ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በህገ መንግሥቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች የራሳ ቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት አላቸው ይላል፡፡ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን ሊያረጋ ግጡበት የሚችሉበት ክልላዊ አወቃቀር ተፈጥሯል፡፡ የማንነት ጥያቄን የመለሰ ህገ መንግሥት አለ። እናም ይህ የግጭት ምክንያት ሊሆን አይችልም" ብለዋል፡፡

ሌላው አሁን ያለው የፌዴራል ስርዓት ብሔሮችና ብሔረሰቦችን መሰረት አድርጎ በመዋቀሩ ምክንያት ኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ተጋጭተዋል የሚል አስተሳሰብ ካለ ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም እየተጋጩ ያሉት ህዝቦቹ ሳይሆኑ የጠባብነትና የትምክህት አስተሳሰብ ያለባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ናቸው፡፡ አሁን ያለውን አወቃቀር እንደ ምክንያት በማድረግ የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ብሔርን ከብሔር ለማቃቃርና ግጭት ለመፍጠር ይጠቀሙበታል እንጂ ብሄሮችና ብሄረሰቦችን መሰረት ተደርጎ የተዋቀረው ስርዓት በራሱ የግጭት ምንጭ አይሆንም ነው ያሉት፡፡

አሁን ያለው የፌዴራላዊ ስርዓት የፌዴራል መንግሥቱ በተለይ ልዩ ድጋፍ በሚሹ አራቱ ክልሎች ጣልቃ በመግባት የሰው ኃይሉን በማስተባበርና በጀትም በመመደብ ከሌሎች ክልሎች ጋር በልማት እንዲመጣጠኑ ላለፉት ዓመታት በርካታ የልማት ሰራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በእነዚህ ስራዎችም ብዙ ለውጦች መጥተዋል፡። እናም ልማት በተስፋፋ ቁጥር ዘላቂ ሰላም መምጣቱ አይቀርም ብለዋል፡፡

‹‹ ክልሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦችን መሰረት ተደርጎ በመዋቀራቸው ምክንያት ወደ ግጭት የገባ የለም፡፡ ይልቁንስ ይህ ሽፋን ይሆንና የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ካለመጠቀም፣ መሬትን የማስፋፋት ፍላጎት፣ ለራስ ብሔር በማድላት በሌላው ላይ ጫና መፍጠር (ዴሞክራቲክ ብሔርተኝነት ካለመጎልበት) ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችም መኖራቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ግጭት ይፈጥራሉ እንጂ ብሔሮችንና ብሔረሰቦችን መሰረት ያደረገ የፌዴራል ስርዓትን መከተላችን አይደለም ግጭት እያስነሳ ያለው›› ሲሉ አብራ ርተዋል- አቶ ሲሳይ፡፡

ግጭቶቹ የህዝብ ግጭቶች አይደሉም፡፡ ህዝብና ህዝብ ተጋጭቶም አያውቅም፡፡ ወደፊትም አይጋጭም፡፡ ሆኖም በየአካባቢው ህዝቡ እንዲጋጭ የሚያደርግ አመራርም ሆነ ግለሰብ መኖሩ ሀቅ ነው፡፡ ስለዚህ የፌዴራል መንግሥቱ እያደረገ ያለው ነገር አንዱ የህግ የበላይነት ማስከበር ነው፡፡ ተጣርቶ በግጭቱ እጃቸው ያለባቸው አመራርም ይሁን ግለሰብ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ በተግባርም ይኸ ስራ መጀመሩን ነው በአብነት የሚጠቅሱት፡፡

በኦሮሚያና በኢትዮ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በተነሳው ግጭት ምክንያት የደረሰው ጉዳት መጠንና የተፈናቀሉት ዜጎችና የደረሰው ጉዳት መጠን ምን ያህል እንደሆነ ገና እየተጣራ ነው፡፡ ተጣርቶ ሲያልቅ የሚገለጽ ይሆናል፡፡ ግጭቱን ለማረጋጋትና ለመግታት በፌዴራል ደረጃ ብሔራዊ ስትሪግ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡ ምርመራ የሚያካሄደው ምርመራ እያደረገ ነው፤ ጸጥታ የሚያስ ጠብቀው ጸጥታ እያስጠበቀ ይገኛል፡፡ ለተፈናቃዮች የእለት ደራሽ ዕርዳታ እንዲያ ገኙም በመደረግ ላይ ነው፡፡ በዘላቂነት የሚቋቋሙበት አቅጣጫም ይቀመጣል፡፡ ግጭቱ ከተከሰተ ጀምሮ ፌዴራል መንግሥቱና ሁለቱ ክልሎች ችግሩን ለመፍታት በመረባረብ ላይ ናቸው፡፡ ችግሩ የተከሰተው ማን ምን ማድረግ ይቀረው ነበር የሚለው ተጣርቶ እያንዳንዱ በየሚዛኑ የሚገመገም ይሆናል ሲሉም ነው አቶ ሲሳይ የተናገሩት፡፡

አቶ ሲሳይ በሚያጋጥመው ግጭት ልክ በየደረጃው የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ የሚሰራ ይሆናል ብለዋል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም በየደረጃው እየፈታን በሄድን ቁጥር በጠባብነትም፤ በትምክህትና በኪራይ ሰብሳቢነት የሚታዩ አመለካከ ቶችንና ተግባራትን የማስተማርና የአቅም ግንባታ ስራ ቀጣይነት ባለው መልኩ ከተሰራና ልማቱም እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር በአጎራባች ክልሎች ያለው ትስስር እየተጠናከረ ስለሚሄድ ግጭትም እየቀነሰ መምጣቱ አይቀርም ነው ያሉት፡፡

 

ጌትነት ምህረቴ

Published in ፖለቲካ

 

በኢትዮጵያ ከታክስ የሚሰበሰበው ገቢ እያደገ ቢመጣም ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ያህል ገቢ እየተገኘ እንዳልሆነ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። የታክስ ገቢ በሚፈለገው መጠን እንዳይሰበሰብ ከሚያደርጉ ዋና ዋና ችግሮች መካከል ደግሞ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር አለመኖር እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት የመስራት ባህል ያለመዳበርም እንደሆኑ ይጠቀሳሉ። በሌላ በኩል በተገልጋዮች ዘንድ የሚስተዋለው ከስራ ኃላፊዎችና ከባለሙያዎች ጋር በጥቅም መተሳሰር፥ ገቢን የመሰወር፥ የኮንትሮባንድ ንግድና የታክስ ማጭበርበር የሚፈለገው የግብር መጠን እንዳይሰበሰብ ምክንያት ሆኗል ይላሉ እነዚህ ባለሙያዎች ።

በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪ የነበሩትና ለ45 ዓመታት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በታክስና ኢንቨስትመንት መምህር በመሆን ያገለገሉት እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዪኒቨርሲቲ እየስተማሩ የሚገኙት ፕሮፌሰር ፍስሀፅዮን መንግስቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት የመስራት ባህል ስላልዳበረ የታክስ ስርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግ እንቅፋት ፈጥሯል በሚለው ሀሳብ ይስማማሉ፡፡

የታክስ ሰብሳቢውና በዩኒቨርሲቲዎች መካከል ያለው በቅንጅት የመስራት ባህል እንጭጭ መሆኑንም ፕሮፌሰሩ በማሳያነት ያቀርባሉ፡፡ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ የነበሩ የ3ኛ ዲግሪ ተመራቂዎች በታክስ ሥርዓቱና አተገባበሩ ዙሪያ ያደረጓቸውን የጥናት ጸሁፎች ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርና ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን እንደተሰጡ ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም ተቋማቱ እነዚህ ጥናቶችን ስራቸውን ለማዘመን እየተጠቀሙባቸው አይደለም ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡

በዩኒቨርሲቲዎች ብዙ ጊዜ በታክስ፣ በጉምሩክና ኢንቨስትመንት ዙሪያ ብዛት ያላቸው ጥናቶች ይደረጋሉ፡፡ ምን ዋጋ አለው በሚመለከታቸው ተቋማትና በዩኒቨር ሲቲዎች መካከል ድልድይ ባለመኖሩ ስንት የተለፋባቸውና መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ እንዲሁም ለፖሊሲ ውሳኔዎች እንደ ግብዓት የሚጠቅሙ ጥናቶች ጭምር መደርደሪያ ማድመቂያ ሆነዋል፡፡ ይህ የሚያሳው የምሁራንን እውቀትና ክህሎት መጠቀም አለመቻሉን ነው የሚል ቅሬታ አላቸው፡፡ እውቀት ያላቸውን ሰዎች በአገር ልማት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ምቹ ሁኔታዎችን ያለመፍጠር የሚጎዳው አገሪቱንና ህዝቧን ነው፡፡ ስለዚህ የታክስ ስርዓቱን ዘመናዊ ማድረግ የሚቻለውና መሰረታዊ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በራስ አቅም በማጠናከርና በመጠቀም ነው የሚል እምነት አላቸው ፕሮፌሰር ፍስሀፅዮን፡፡

‹‹የታክስ ስርዓትን ለማዘመንና ገቢውን ለማሳደግ ታክስ ሰብሳቢው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጀትና በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ምንም ጥርጥር ባይኖረውም በስብሰባዎች ላይ የውይይት አጀንዳ ከማድረግ ውጭ በመተግበር ረገድ ዳገት ሆኖብናል ፡፡ ስለዚህ በጥናት ላይ የሚሰማሩ ኢትዮጵያውያንና ፖሊሲ አውጪዎች በቅንጅት መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን የቅንጅት ድልድይ መፍጠር ካልተቻለ ለፍቶ መና ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ጥናት ሲጠና ጊዜ፣ ሀብትና ምርምር ይጠይቃል፡፡ ይህ የተለፋበት የምርምር ስራ ተግባር ላይ ካልዋለ ለአገሪቱም ሆነ ለተመራማሪው ኪሳራ ነው የሚያስከትለው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ተባብረን ለአገርና ለወገን ስንል በቅንጅትና በቅን ልቦና ልንስራ ይገባል›› ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ፡፡

በታክስ ዙሪያ ጥናት ሊደረግ ይችላል እነዚህ ጥናቶች ለአገራችን ገቢ ለማሰባሰብ ምን ያህል ይረዳሉ፤ ተጨባጭነታቸውስ የሚሏቸው ነገሮች ወሳኝ ናቸው፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ከገንዘብ ሚኒስቴር ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከምሁራን ጋር ያላቸው ግንኙነት የበለጠ መጠናከር አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም መሪ ለሌሎች አርአያ የሚሆንና የተግባር ሰው መሆን አለበት የሚል እምነት አላቸው ፕሮፊሰሩ፤ ተመራማሪዎችም ሆኑ የፖሊሲ አውጭዎች በተግባር የተደገፈ ስራ መስራት አለባቸው፡፡ እኔ ለአገሬ ምን አበርክቻለሁ፣ ከዚህ ዓለም ስለይ ህብረተሰቡ የሚያስታውሰኝ ትውልድ ተሻጋሪ ምን አይነት ስራ ትቼ አለፍኩ ልንል ይገባል ይላሉ፡፡

እንደ ፕሮፌሰር ፍስሀፅዮን ገለጻ፤ በታክስ አሰባሰብ ስርዓቱ የግልጸኝነትና የተጠያቂነትን አሰራር ከሌለ ህብረተሰቡ ለምን ታክስ እከፍላለሁ ሊል ይችላል፡፡ ታክስ ከፖለቲካ፣ ከህብረተሰቡ ባህልና አስተሳሰብ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ታክስ ለአገር ግንባታ የሚውል ገንዘብ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን የሚሰበሰበው ገንዘብ የሚውለው ለትምህርት ቤት፣ ለመንገድ፣ ለጤናና ለሌሎች መሰረተ ልማቶች መዋሉን በአይኑ ሲመለከት እውነትም ለአገርና ለወገኔ ልማት ይውላል ብሎ በፈቃደኝነት ይከፍላል፡፡ በአንጻሩ ገንዘቡን ሙሰኞች የሚቀራመቱት ከሆነ ታክስ ለመክፍል ወደ ኋላ ያፈገፍጋል፡፡ ለዚህ በመጀመሪያ በታክስ አሰባሳብ ላይ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት አሰራርን መዘርጋት ይገባል፡፡

ታክስ ከህብረተሰቡ ባህል፣ አስተሳሰብና ገቢ እንዲሁም ከአገሪቱ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ህግ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በአጼ ኃይለሥላሴ ጊዜ ኢኮኖሚው እምብዛም ስላልዳበረ የታክስ ስርዓቱ ውስብስብ አይደለም፡፡ በደርግ ጊዜም ታክስ ከፍተኛው የመንግስት ገቢ ምንጭ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ የግል ኩባንያዎች በመንግስት ስር እንዲሆኑ ተደርጓልና፡፡ አሁን ደግሞ የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ነው የምንከተለው፡፡ መንግስት በነጻ ገበያ ስም ነጻ ብዝበዛ እንዳይደረግና ፍትሀዊ የታክስ አከፋፈል ስርዓት እንዲኖር መቆጣጠር ይኖርበታል፡፡ ከሚቆጣጠርበት መንገድ አንዱ ደግሞ ታክስ ነው፡፡ ታክስን ክፈሉ ብሎ በጫና ማስከፈል ተገቢ አይደለም፡፡ ቅድሚያ ውይይት ማድረግና ህብረተሰቡን ማሳመን ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ጥሩ የታክስ አስተዳደር፣ ፖሊሲና ህግ አላት፡፡ መንግስት እነዚህን ወደ ተግባር ሊተረጉማቸው ይገባል ነው ያሉት፡

ፕሮፌሰሩ እንዳሉት፤ ሌላው ችግር የአፈጻጸም ድክመት ነው፡፡ የሰው ሀይል ልማት ስርዓት ካልተበጀ ዘመናዊ ታክስ ስርዓት እዘረጋለሁ ማለት የማይታሰብ ነው፡፡ አንድን አሰራር አሜሪካ ጀርመን አሊያም ሌላ አገር ስለተገበሩትና ውጤታማ ስለሆኑበት ብቻ አገራችን ላይ ይሰራል ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የአገራችን ማህበረ ኢኮኖሚ የተለየ ነው። ስለዚህ ዘመናዊ የታክስ ስርዓት መዘርጋት የምንችለው የአገራችንን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ መሰረት ባደረገ መልኩ መሆን አለበት፡፡

ታክስ መሰብሰብ በጣም አስቸጋሪ የሆነ የመንግስት ስራ ነው፡፡ ምክንያቱም ታክስ ከፋዩ በከፈለው ልክ በቀጥታ ጥቅም የማያገኝበት በመሆኑ ማንም ሰው ታክስን በፈቃደኝነት ለመክፈል ይቸገራል የሚሉት በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አማካሪ የሆኑት አቶ ፋንታሁን በለው ናቸው። የታክስ ጥቅም ግን የሚታወቀው በተዘዋዋሪ መንግስት በሚያካሂዳቸው የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችና አገልግሎቶች መሆኑን በመጥቀስ የስራውን አስቸጋሪነት ይገልጻሉ።

ጥቅሙ ዘግይቶ የሚገኝ በመሆኑ በፈቃደኝነት የመክፈሉና ታክስን መሰብሰብ አስቸጋሪ ስራ ያደርገዋል ይላሉ፡፡ ስለዚህ ይህን አስቸጋሪ ስራ ደግሞ መንግስት ብቻውን ሳይሆን የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ሲሳተፉበትና ሲረባረቡበት ነው ውጤታ መሆን የሚቻለው፡፡ በታክስ ላይ የሚደረጉ የምርምር ስራዎች ደግሞ ለአገሪቱ የታክስ አሰባሰብ መጎልበት ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ስራዎች በምርምርና በስርጸት ላይ እንዲመሰረቱ ያደርጋል፡፡ ይህም ዘላቂነት ያለው የታክስ ማሻሻያ ለማድረግ ያስችላል፡፡ እናም አሉ ከምርምር ተቋማት ጋር አብሮ የመስራቱ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ የታክስ ስርዓት የሚለካው ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው ውስጥ ምን ያህል ታክስ ይሰበሰባል የሚለው ሲመዘን ነው የሚሉት አቶ ፋንታሁን፤ ከዚህ አኳያ ኢኮኖሚው እያደገ ቢሄድም በዚሁ ልክ ታክሱ ዕድገት እያሳየ አይደለም ባይ ናቸው፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡን አሳምኖ፣ መብትና ግዴታውን አሳውቆ በበቂ ደረጃ ታክስን ለመሰብሰብ ይቻላል የሚል እምነት አላቸው፡፡

እንደ አቶ ፋንታሁን ገለጻ፤ በታክስ አሰባባሰብ የሚታው አንዱ ትልቁ ችግር የታክስ ጫናው ከፍተኛ ሆኖ ሳይሆን ታክስ ከፋዩን በታክስ አሰባሰብ ዙሪያ ግንዛቤ የመፍጠር ክፍተት መኖሩ ነው፡፡፡ የኢትዮጵያ የታክስ ስርዓት በመጀመሪያ ደረጃ መነሻው ታክስን በፈቃደኝነት መክፍል ላይ ነው፡፡ ታክስ ከፋዩ ይህን ያህል ገቢ አገኝቻለሁ ይህን ያህል ደግሞ ታክስ መክፈል አለብኝ ብሎ ሪፖርት የሚያደርገውን መረጃ ነው መሰረቱ የሚያደርገው፡፡ ትክክለኛነቱ የሚረጋገጠው ቀጥሎ ነው፡፡

በታክስ አሰባሰብ ስርዓት ላይ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ያለበት አሰራር ካልተዘረጋ ታክስ ከፋዩ ገንዘባችን በሙሰኞች አማካኝነት ለግለሰቦች መጠቀሚያ ሊውል ይችላል የሚል አስተሳሰብ ሊኖረው ይችላል፡፡ ይህ አመለካከት የሚፈጠረው ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ ነው ይላሉ፡፡ ከታክስ የሚሰበሰበው ገንዘብ እንዴት ነው ስራ ላይ የሚውለው? ምን ውጤት አመጣ? የሚለውን ተጨባጭ ሀቅ ለታክስ ከፋዩ በማሳወቅ ትክለኛውን አስተሳሰብ እንዲይዝ ማድረግ የታክስ ሰብሳቢው መስሪያ ቤት ተግባር ነው፡፡ ምክንያቱም ታክስ የሚሰበሰብበትና ወጪ የሚሆንበት ስርዓት አለው፡፡ ለአገሪቷ ዓመታዊ በጀት የሚመደበው አብዛኛው ከታክስ ከሚገኝ ገቢ ነው፡፡

ዜጎች በአገኙት ገቢ መጠን ልክ ታክስ የማይከፍሉ ከሆነ ኢፍታዊነትን ያሰፍናል ያሉት አቶ ፋንታሁን፤ ስለዚህ መንግስት ትልቁን ስራ መስራት ያለበት የታክስ ስርዓቱን ፍትሀዊ ማድረግ ላይ ነው። ሁሉም በገቢው መጠን እንዲከፍል ማድረግ ይገባል፡፡ አንዱ ትልቁ ድክመት የሚፈጠረው እዚህ ላይ ነው፡፡ሁሉም በገቢው መጠን እንዲከፍል ከተደረገ ዜጎች በፈቃደኝነት ታክስ የመክፈል ባህላቸው እየጎለበተ ይሄዳል ሲሉ አስተያታቸውን ሰጥተውናል፡፡

በፖሊሲ ዘመናዊና ፍትሀዊ የታክስ ስርዓት ለመዘርጋት ጥረት ቢደረግም በአፈጻጸም በኩል ግን ትልቅ የማስፈጸም የአቅም ችግር መኖሩን አልካዱም፡፡ በተለይ አሰራሩ ወደ ታች ሲወርድ ምን ያህል በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ይሆናል የሚለው ጥያቄ ይፈጥራል፡፡ ብዙ ጊዜ በኢትዮጵያ ትክክለኛ ፖሊሲዎች ይወጣሉ፣ ስትራቴጂዎች ይቀረጻሉ፡፡ ሆኖም እነዚህን በትክክል የመተግበሩ ላይ ድክመት መኖሩ በግልጸ የሚታይ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ ሁልጊዜ ይህ ችግር መኖሩ ቢገለጽም ማሻሻል አልተቻለም፡፡ ማሻሻል ግን ግዴታችን ነው የሚሆነው ሲሉም አሳስበዋል ፡፡

በመጀመሪያው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዓመት መነሻ ላይ በ35 ቢሊዮን ብር ተወስኖ የነበረው ዓመታዊ የታክስ ገቢ በ2007 በጀት ዓመት ወደ 186 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ዕድገት ያሳየ ቢሆንም አሁንም ከአገራዊ አጠቃላይ ምርት (ጅዲፒ) አንጻር ያለው ድርሻ 13 በመቶ እንኳን ሊደርስ አልቻለም። ስለዚህ ብዙ ስራ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡

 

ጌትነት ምህረቴ

 

 

 

 

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

 

በበርማ ግዛት በሰሜናዊ ራኪን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ቀያቸውን ጥለው እንዲፈናቀሉ ምክንያት በሆነውና እአአ በነሐሴ 25 ቀን 2017 የተጀመረው ቀውስ አሜሪካ እንደሚያሳስባት ገልጻለች፡፡ የተፈናቀሉና የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው። የበርማ ደህንነት ሐይል የሮሂንጂያ ማሕበረሰብ ጎሳና ሌሎች አናሳዎችም ጨምሮ የንጹሐኑ ህይወት ሊታደጋቸው አለመቻሉ ነው፡፡ አሜሪካ እየደረሰ ባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት እጅግ ማዘኗን ብትገልፅም ችግሩን ግን መቀነስ አልቻለችም። የበርማ የደህንነት ባለስልጣናት ህግን ማክበር፣ ግጭቱን ማስቆምና የንጹሃኖቹን መፈናቀል ማስቆም እንዳለባቸው ጥሪ ግን አድርጋለች፡፡

በተጨማሪ የበርማ ጸጥታ ሃይል ከተመረጠው መንግስት ጋር በመሆን የራኪን ምክር ቤት አማካሪዎች ተግባራዊ ለማድረግ በጋራ መስራት እንዳለበትም አሳስባለች፡፡ የበርማ መንግስት እያደረገው ያለው በተቻለው መጠን ፈጥኖ የሰብአዊ እርዳታ የማቅረብ ቁርጠኝነትም አሜሪካ ታደንቃ ለች፡፡ አብዛኞቹ ተፈናቃይዎች ወደ ጎረቤት አገር ባንግላዴሽ የተሰደዱ ሲሆን የባንግላዴሽ መንግስትም ያደረገላቸው የሰብአዊ እርዳታ የሚመሰገን ነው፡፡

በበርማ የቡድሂስቶች ስፍራ በሚገኙ ሙስሊሞች ላይ የተፈጸመውን ጭፈጨፋ የዋይት ሃውስ አስተዳደር ያወግዛል፡፡ የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊዋ የሆኑት ኡንግ ሰን ሱ ኪይ በበርማ ሙስሊሞች የሚፈጸመውን የዘር ማፅዳት ተግባር የመሩት ሲሆን ተግባሩን ለማስቆም ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዳቸው ግን የዓለም ማሕበረሰብን አስቆጥቷል፡፡ በነሐሴ መጨረሻ አካባቢ ከሁለት ሺ እስከ ሶስት ሺ የሚደርሱ የራኪን ግዛት ነዋሪ ሙስሊሞች መገደላቸው የአውሮፓ ሮሂንግያ ምክር ቤት ጠቁሟል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ በርማ ግጭቱን ማስቆም እንዳለባት ጠይቋል፡፡ ምክንያቱም ቀጠናውን ያለማረጋጋት ሁኔታ ተፈጥሯል በዚህም የተባበሩት መንግስታት እርዳታ ድርጅቶች በስፍራው አስፈላጊውን ሰብአዊ እርዳታ እንዳያደርጉ መከልከላቸው ዘጋርድያን ድረገጽ ጠቅሷል፡፡ የዋይት ሃውስ አስተዳደር በተመሳሳይ በበርማ በተፈጠረው ግጭት ሰለባ ለሆኑ ዜጎች ሰብአዊ እርዳታ ማቅረብና ግጭቱ በተፈጠረበት አካባቢ ለሚድያ በአፋጣኝ ክፍት ማድረግ እንዳለበት አሳስቧል፡፡

የበርማ መከላከያ ሰራዊቱ የበርማ ሙስሊሞች በሚሰደዱበት መንገዳቸው ላይ ፈንጂ በመቅበር ለእልቂት እየዳረጋቸው ነው በማለት አሚኒስቲ ኢንተርናሽናል ይከሳል፡፡ ለዚህም በባንግላዴሽ አዋሳኝ አካባቢ በፈንጂ ፍንዳታ የቆሰሉ በርካታ ዜጎች ተገኝቷል ብሏል፡፡ በርማ እንደነ ሰሜን ኮሪያና ሶርያ በግልጽ በመሬት ላይ የተቀበረ ፈንጂ ከሚጠቀሙ ጥቂት አገራት አንዷ ነች በማለት አሚኒስቲ ይከሳል፡፡

የባንግላዴሽ የድንበር ጠባቂ ሌተናንት ኮሎኔል ኤስኤም አሪፉል ኢስላም በትንሹ ሦስት የሚሆኑ ሮሂንግያውያን በፍንዳታው መጎዳታቸውን ተናግረዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ለማነጋገርና ሃሳብ ለማግኘት የበርማ መንግስት ቃለአቀባይ ጋር ቢደውሉም መልስ ማግኘት አለመቻላቸው አሚኒስቲ ጠቁሟል፡፡ የመከላከያ ሃይል ቃለአቀባይም ቢሆን የበላይ አለቆቻቸው ማብራሪያ ሳይሰጡ ምንም መናገር እንደማይፈልጉ ገልጸዋል፡፡

የሮሂንግያውያን ቀውስ እየተባባሰ በመምጣቱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ስደተኖች ወደ ባንግላዴሽ መግባታቸውን የተባበሩት መንግስታት አስታውቋል፡፡ በበርማ የመከላከያ ሃይልም ጭምር በሚደርስባቸው ጥቃት መቋቋም ባለመቻ ላቸው ቀያቸው ጥለው ይሰደዳሉ እንዲሁም ቤታቸው ተቃጥሎ ባቸው፣ ወገኖቻቸው ተገድሎባቸው በግፍ እየተሰደዱ መሆና ቸውን የተገነዘበው የተባበሩት መንግስታት ጉዳዩን ግልጽ የዘር ማፅዳት ተግባር ነው ብሎታል፡፡

የሚኖርበት አካባቢ የተቃጠለባቸው አንዳንድ ስደተኞች ሀገሪቱን ለቀን እንድንወጣ የሚፈልጉ መሆናቸውን ያሳያል ሲሉ መናገራቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባ ጠቅሷል፡፡ በጀኔቫ ባደረገው አጠቃላይ የድርጅቱ ስብሰባ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት የተፈናቃዮች ቁጥር 370 ሺ የሚደርስ ሲሆን ይህ አሃዝም በግምታዊ አማካይነት የተወሰደ ቢሆንም ቁጥሩ በፍጥነት በመጨመር ላይ እንደሚገ ኝም ጠቁሟል፡፡

በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ረጂም ርቀት በማቋረጥ በምግብ እጥረትና ድካም ከሚያጋጥማቸው በተጨማሪ የሰብአዊ እርዳታ አጥተው ይባስ ብሎ የወንዝ አሸጋጋሪዎች ለአንድ ሰው ለማሻገር 122 ዶላር የሚሆን ያስከፍሏቸዋል፡፡ በርማ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሙስሊም ነዋሪዎች ሀገር የሌላቸው እንዲሁም የሀገሪቱ መንግስት ከባንግላዴሽ በህገ ወጥ ተሰድደው የመጡ ናቸው በማለት ይፈርጃቸዋል፡፡

አናሳ ቁጥር አላቸው ተብለው የሚ ታወቁት ቡድን ለአስርት ዓመታት ያክል አድልዎና መገለል ሲደርስባቸው የቆየ ሲሆን ሮሂንግያ ከቡድሂስቶች ጋር በበርማ ምዕራብ ራኪን ግዛት እአአ በ2012 .. ከተታኮሱ በኋላ ይበልጥ እየተባባሰ መጥቷል፡፡ በወቅቱ ከ100ሺ በላይ በአንድ ካምፕ ውስጥ ታቅበው የስራ ዕድል የማግኘት፣ የመንቀ ሳቀስና የመማር ዕድላቸው በጽኑ ታግደው ነበር፡፡

አንዳንድ ሙስሊም ስደተኞቹ በስፍራው የቆየ ብቅ ድርግም የሚል ግጭት ቢኖርም የአሁን ግን በጣም የተለየ መሆኑ ይገልጻሉ፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ግጭት በሁለቱም ማለት በቡድሂስት ተከታዮችና በታጠቁ የመከላከያ ሃይል ጥቃት ስለተፈጸመባቸው መሆኑ ጠቁሟል፡፡

ይህ በአጭር ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተጨፈጨፉበትና በከፍተኛ ቁጥር በእግርም በአውሮፕላንም ወደ ባንግላዴሽ እየተሰደዱ ያሉ ሙስሊሞች የዓለም ማሕበረሰብ ምንም የደረሰላቸው ነገር አለመኖሩ እየተገለጸ ነው፡፡

በሌላ በኩል በተባበሩት መንግስታት ይሁን በአሜሪካ በበርማ ማይንማር ላይ የሰጡት ጠንካራ የማዕቀብ ይሁን ተመሳሳይ እርምጃ የለም ይህ ደግሞ አንዳንድ ተቺዎች በሰብአዊ አያያዛቸው ፍትሐዊነት የጎደለው መሆኑን ያብራራሉ፡፡ ፕሬስ ቲቪ በድረገጹ እንደገለጸው አሜሪካ በማይንማር ሙስሊሞች ጥቃት ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማት ብትገልጽም በድርጊቱ ፈጻሚ አካላት ላይ ግን ምንም ያለችው ነገር አለመኖሩን ይተቻል፡፡

 

በሪሁ ፍትዊ

Published in ዓለም አቀፍ

 

በዘመናችን አወዛጋቢ የማንነት መገለጫዎች ሆነው የወጡት ቋንቋ (የብሔር ብሔረሰብ ጉዳይ) እና ሃይማኖት ናቸው። እነዚህ በማንነት ጥያቄ ላይ ተመስርተው የሚነሱ ውዝግቦች ደግሞ መፍትሄ የሚሹ ፖለቲካዊ ጉዳዮች መሆናቸውን መቀበል የግድ ነው። ለዚህ ጥያቄ በኢትዮጵያ ለሦስት ሺህ ዘመናት ሠፍኖ የቆየው የመንግሥት አስተዳደር እና ሥርዓት ተገቢውን ምላሽ መስጠት አልተቻለውም። በዚህም ምክንያት ጉዳዩ የውዝግቦች እና የግጭቶችን መንስኤ በመሆን ለረጅም ዘመናት ቆይቷል። በ1966 ዓም የፈነዳው ህዝባዊ አብዮት ለእነዚህ አወዛጋቢ የማንነት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የጀመረ ነበር ማለት ይቻላል።

ለእነዚህ ፖለቲካዊ ውዝግቦች በሣል የሆነ ትንተና በመስጠት ችግሮቹን አንጥሮ በማውጣት ረገድ ደግሞ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ፋና ወጊ ነበር ማለት ከእውነት የራቀ ሊሆን አይችልም። በ1950ዎቹ መጨረሻና በ1960ዎቹ መጀመሪያ በዋነኛነት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የነበሩ ተማሪዎች አገሪቱ በመሳፍንታዊ አገዛዝ ስር ወድቃ ህዝቦቿም ለሠቆቃዊ ህይወት መዳረጋቸውን አፅንኦት ሠጥተው የገለጹት ጉዳይ ነበር።

ሥርዓቱ የብሔሮችን እና የሃይማኖት ብዝሃነትን ባለመቀበል የአንድ ሃይማኖት እና የሰሜነኞች ባህልና ቋንቋ በአገሪቱ ተንሠራፍቶ መገኘቱ የአገሪቱ ቁልፍ ችግር እንደነበር በማስገንዘብ፤ ይህ ሁኔታ ተለውጦ የህዝቦች እኩልነት እና ነፃነት መረጋገጥ አለበት የሚል መከራከሪያ ነበር። ይህ ሀቅ እውን መሆን ባልቻለበት ሁኔታ አገሪቱ ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት እንደዚሁም ከአመፅ እና ብጥብጥ እንደማትወጣ ተማሪዎቹ አፅንኦት ሠጥተው ያሳሰቡት ጉዳይ ነበር።

ይህን መሠሉ ፖለቲካዊ ጥያቄ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግለቱን እየጨመረ መጥቶ በ1966 ግብታዊው የኢትዮጵያ አብዮት እንዲፈነዳ ምክንያት ሲሆን በውጤቱም የመንግሥት ሥልጣን ከመሳፍንታዊ አገዛዝ ወደ ወታደራዊ አገዛዝ እንዲቀየር አደረገ፡፡ አብዮቱን እጅግ ፈጣን በሆነ ሁኔታ ውስጥ የተከናወነ ሂደት የመሆኑ ጉዳይ ደግሞ ለህዝባዊ አመፁ ምላሽ እንሰጣለን ብለው ለመጡት የወታደራዊ ቡድን አመራሮች ከመቶ አመታት በላይ ቁልፍ ችግር የነበረው የመሬት ጥያቄ ላይ ሥር ነቀል እርምጃ እንዲወስዱ ምክንያት ሆናቸው። በዚህም የአርሶ አደሮች የመሬት ባለቤትነት ጥያቄን ቢመልስም የምርቱ ነጻ ተጠቃሚ ማድረግ ግን ሳይቻለው ቀረ።

ከወታደራዊው መንግስት ውድቀት በኋላም ኢትዮጵያ የመሬት ባለቤትነትን በህዝብና በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲሆን በማድረግ፤ እንዲሁም የምርት ነጻ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ያልተመለሱ የመሬት ጥያቄዎችን መመለስ ተቻለ። በዚህም በአፍሪካ በዋነኛነትም ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ስኬታማ ስራን በማከናወን በአርአያነት የምትጠቀስ አገር እንድትሆን አስችሏታል። የመሬት በመንግሥት እና በህዝብ ይዞታ ሥር የመገኘት ጉዳይ ይህን ሃብት በፍትሃዊ መንገድ ለመጠቀም ከማስቻሉም በላይ ዛሬ በክልሎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል የምናያቸውን የኢኮኖሚ አብዮቶችን ለማቀጣጠል ብሎም ለወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ እየተጫወተ ያለው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

የመሬት በመንግሥት እና በሕዝብ ቁጥጥር ሥር መዋል በቻይና እየተጫወተ ያለውን አብነት ብንመለከት፤ በአንድ የቻይና ግዛት አንድ ግዙፍ የቡና ማምረቻ እና ማከፋፈያ ኩባንያ መሬትን ከአርሶ አደሮች በሊዝ ከተከራየ እና በእርሻው ውስጥም አርሶ አደሮቹን በቅጥር ሠራተኛነት በማቀፍ አስደናቂ የቡና እርሻን ሲያካሂድ ከእርሻው የሚያገኘውን የግብርና ውጤት በአካባቢው ባስገነባው ግዙፍ ፋብሪካ ውስጥ ያለቀለት የኢንዱስትሪ ውጤት በማድረግ አለም አቀፍ የቡና ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ መውጣት ችሏል።

ይህን መሰሉ ተግባር አርሶ አደሩንም ሆነ ባለሀብቱን በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ አሠራር በመሆኑ በሌሎች አገራትም ተግባራዊ ለማድረግ የመሬት በመንግሥት እጅ ውስጥ መገኘት ወሳኝ ይሆናል። ለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የሚያደርገው አስተዋጽኦንም በተመሳሳይ መገንዘብ ይቻላል። ኢትዮጵያ ከዚህ መሰሉ የቻይና ተመክሮ ልምድ በመውሰድ በአርሶ አደሮች እጅ በባህላዊ መንገድ የሚካሄድ ግብርናን ከባለሀብቶች ጋር በመቀናጀት ወደ ዘመናዊ አግሮ ኢንዱስትሪ በመቀየር አገሩም ሕዝቡም ተጠቃሚ በማድረግ የምትችልበት ዕድል አላት።

በአንፃሩ በአፍሪቃ መሬት በግል ባለሀብቶች ይዞታ ሥር የመገኘቱ ጉዳይ እነ ደቡብ አፍሪካንም ሆነ ጋናን የመሳሰሉ በኢኮኖሚ ዕድገት እና በመልካም አስተዳደር በመልካም የሚጠቀሱ አገሮች ከዚህ ዕዳ ገና ያልተገላገሉ ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦንብ ታቅፈው የሚሄዱ አገሮች ናቸው። በዑጋንዳ እና ጋናን በመሳሰሉ የአፍሪካ አገራት መሬት በአካባቢ ቺፍስ (የጐሣ መሪዎች) እጅ ሥር መገኘት ይህን ሀብት ተጠቅሞ ዘለቄታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ለመዘርጋት ከተጋረጡባቸው ዋነኛው ተግዳሮቶች መካከል የመሬት ጥያቄ ዋነኛው ጉዳይ ነው።

የዚምባብዌው መሪ ሮበትር ሙጋቤ የመሬት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በወሰዱት ሥር ነቀል እርምጃ ነጭ ዚምባብዌያዊያን እና የአለም አቀፍ ተቃዋሚ ኃይሎች ላይ በጣለው የኢኮኖሚ ማዕቀብ አገሪቱ ወደ ዕድገት ፊቷን እንዳታዞር ዋነኛው እንቅፋት ሆኖባት ይገኛል። ይህ የሙጋቤ እርምጃ ለሌላው የአፍሪካ አህጉር መጥፎ ምሳሌ ይሆናል ተብሎ በመገመቱ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ጠንካራ እርምጃ በመውሰድ መንግሥቱን ሲያዳክሙት ሌሎች የአፍሪካ መሪዎች ደግሞ ከዚህ መሰሉ ድርጊት እራሳቸውን ቆጥበው የሕዝባቸው የመከራ ዘመን እንዲቀጥል አድርጓቸው ይገኛል።

የኢትዮጵያው የ1966 አብዮት የመሬት ጥያቄ ላይ የወሰደው ሥር ነቀል እርምጃ ዓይነት በብሔር እና በሃይማኖት የማንነት ጥያቄ ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ በጥገናዊ ለውጥ ሸፋፍኖቸው ሊያልፍ ፈለገ። በእርግጥ መንግሥት እና ሃይማኖት ሁለት የተለያዩ አካላት ናቸው። መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም። ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ ሊገባ አይገባውም የሚለውን መርህ መከተሉ ለበርካታ ዘመናት ሥር ሰዶ የቆየውን የማህበረሰባችን በኋላ ቀር አመለካከት ለመስበር የተጫወተው ሚና እንዲህ በቀላሉ ልናየው የሚገባ አይደለም።

በብሔር ብሔረሰብ ጥያቄ ዙሪያ አብዮቱ ጉዳዩን በጥገናዊ ለውጥ በማለፍ ብቻ ሳይወሰን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚነሱ የመብት ጥያቄዎችን የአገር አንድነት የሚያናጉ የገንጣይ ተገንጣይ ጥያቄዎች አድርጐ በመፈረጁ ችግሩን በጠመንጃ ኃይል ብቻ ለመፍታት ሙከራ አደረገ። በውጤቱም ወታደራዊው መንግሥት ሥልጣኑን በጠመንጃ ኃይል አጥቶ ሲሸነፍ የኤርትራም ችግር ከኢትዮጵያ ተለይታ ሉዓላዊነት አገር በመሆን ተጠናቀቀ።

የብሔር ብሔረሰቦችን ጉዳይ አገራችን ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በፌዴራላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ምላሽ ለመስጠት ደፋ ቀና እያለች ያለችበት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ደርሳለች። ውጤቱ በተራዘመ ሂደት የሚታይ እንጂ በአጭር ጊዜ በተሟላ መልኩ ሊከናወን የሚችል ተግባር አይደለም። የኢኮኖሚ ዕድገት እና ኢንዱስትሪያላ ይዜሽን የከተሞች ዕድገት እና በዕውቀት የበለፀገ ማህበረሰብ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነቡ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማስፈጸሚያ ተቋማት በእጅጉ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች ናቸው። በአጠቃላይ የካፒታሊስት ሥርዓት ለፌዴራል የአስተዳደር ሥርዓት ቅድመ ሁኔታ ነው ማለት ይቻላል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ከአድዋው ፀረ-ቅኝ አገዛዝ አንፀባራቂያዊ ድል በተጨማሪ በመሬት ሥሪት ላይ የተጐናጸፈችው ውጤታማ ሥራ ለአፍሪካውያን ፋና ወጊ ተግባር ሆኖ እንደተገለጸው ሁሉ፤ የፌዴራል ሥርዓትን በመዘርጋት እያደረግን ያለነው ጥረት ለችግሮቻችን የራሳችን የሆነ አፍሪካዊ መፍትሔ በመስጠትም ምሳሌ እንደሚያደርግን ይታመናል። የተጀመረው የፌዴራሊዝም ስርዓት በየጊዜው እየዳበረ የሚሄድ ከአደጉት አገራትም የሚቀዳ ተሞክሮችንም ወደ ተግባር በመቀየር ውጤታማ መሆን የሚያስችለን ነው። ይህንን ስርዓት እስከጫፍ በመውሰድና ውጤታማ በማድረግ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን አንድ ተጨማሪ ተመክሮ ማበርከት የምንችልበት ዕድሉ ከፊታችን ይጠብቀናል።

 

ሮባ ቶኪቻው

Published in አጀንዳ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።