Items filtered by date: Thursday, 05 October 2017

የዓለማቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በየዓመቱ የሚያከናውነው የምርጥ አትሌቶች ሽልማት በእግር ኳሱ «ባሎን ድ ኦር» ተብሎ ከሚጠራው ታላቅ ሽልማት እኩል በአትሌቲክሱ ትኩረት የሚሰጠው ነው። ለዚህም በውድድር ዓመቱ መጨረሻ አካባቢ ዓለማቀፍ ማህበሩ በአትሌቲክስ ባለሙያዎችና በስድስት ክፍለ ዓለማት ባሉት ተወካዮች አማካኝነት ለምርጥ አትሌቶች ሽልማት አስቀድሞ አስር እጩዎችን ይመርጣል። ከወር በኋላ ሞናኮ ላይ በሚከናወነው የሽልማት ስነስርዓት የሚፎካከሩ አስር አትሌቶች ስም ዝርዝር ከላይ በተጠቀሰው መሰረት ከትናንት በስቲያ ታውቀዋል።

ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በርካታ አትሌቶችን በሁለቱም ፆታዎች ከአስሩ እጩዎች መካከል ከማስመረጥ አልፋ ሽልማቱን በተደጋጋሚ ያሸነፉ አትሌቶችን ብታገኝም ዘንድሮ ከአልማዝ አያና በስተቀር በአስሩ እጩዎች ዝርዝር ውስጥ መካተት የቻለ አትሌት ሳታገኝ ቀርታለች። የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮኗ አልማዝ በ2017 የውድድር ዓመት ለአስራ አንድ ወራት ያህል ከውድድር ርቃ ብትቆይም ባለፈው የለንደን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ በአስር ሺ ሜትር የወርቅ፤ በአምስት ሺ ሜትር ደግሞ የብር ሜዳሊያ ማጥለቋ ለእጩነት አብቅቷታል።

በውድድር ዓመቱ ምንም አይነት ጉዳት ሳያስተናግዱ በተለያዩ ውድድሮች በተለይም በዳይመንድ ሊግ ሲሳተፉ የቆዩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በእጩዎቹ ዝርዝር ውስጥ መካተት አልቻሉም። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዳይመንድ ሊጉ የዓመቱ አሸናፊዎች ተርታ ሳይካተቱ መቅረታቸውም ከእጩዎቹ ዝርዝር ውስጥ ላለመካተታቸው አንዱ ምክንያት ነው።

በለንደኑ ቻምፒዮና በአምስት ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀው ሙክታር ኢድሪስ በእጩዎቹ ዝርዝር ውስጥ ያልተካተተበት ምክንያትም በዳይመንድ ሊግ አጠቃላይ አሸናፊ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደሆነ መገመት ይቻላል።

ያለፈውን ዓመት የምርጥ አትሌቶች ሽልማት ማሸነፍ የቻለችው አልማዝ ምንም እንኳን በውድድር ዓመቱ ከለንደን ቻምፒዮና ሁለት ውድድሮች ውጪ መካፈል ባትችልም ከጉዳት ተመልሳ በአጭር ጊዜ ዝግጅት አስር ሺ ሜትሩን 30:16.32 በሆነ የዓመቱ ፈጣን ሰዓት ማሸነፏ ዳግም ለሽልማቱ እንድትታጭ አድርጓታል። ከዚህ በተጨማሪም በአምስት ሺ ሜትር እዚያው ለንደን ቻምፒዮና ላይ የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ መቻሏ መራጮቹን ከእጩዎቹ ዝርዝር ውስጥ እንዲያካትቷት አስገድዷቸዋል።

2016 የውድድር ዓመት የአትሌቲክሱ ዓለም ከተመለከታቸው ድንቅ አትሌቶች መካከል አንዷ አልማዝ አያና ነበረች። በሪዮ ኦሊምፒክ በአስር ሺ ሜትር 29:17.45 የሆነ የዓለም ክብረወሰን በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችው አልማዝ በአምስት ሺ ሜትርም የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት ስትሆን የዳይመንድ ሊግ አጠቃላይ አሸናፊም ጭምር ነበረች።። በሮም ዳይመንድ ሊግ ላይ በአምስት ሺ ሜትር 14:12.59 የሆነ ሁለተኛው የዓለማችን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገቧም በውድድር ዓመቱ የሚጠቀስ ታላቅ ስኬቷ ተደምሮም የዓመቱ ምርጥ አትሌት ሽልማት አሸናፊ ለመሆን በቅታለች።

አልማዝ በሪዮ ኦሊምፒክ በተለይም በአስር ሺ ሜትር ስታሸንፍ ለሃያ ሦስት ዓመታት በቻይናዊቷ ዋንግ ጁአ ተይዞ የቆየውን የዓለም ክብረወሰን በአስራ አራት ሰከንዶች ማሻሻሏ ሽልማቱን ለማግኘቷ ዋና ምክንያት ነበር። አልማዝ በወቅቱ አስር ሺ ሜትርን ለመጀመሪያ ጊዜ በሮጠችበት የሄንግሎ የሰዓት ማሟያ ወይንም ሚኒማ ውድድር ላይ ያስመዘገበችው 30:07 ሰዓት በርቀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሮጠች አትሌት የተመዘገበ የዓለም ክብረወሰን ሰዓት ሆኖ ተይዟል።

2007 እኤአ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና እንዲሁም በ5ሺ ሜትር ከፍተኛ ስኬት ያገኘችው መሰረት ደፋር በወቅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ኮከብ አትሌትነት የተሸለመች ኢትዮጵያዊት ሴት አትሌት መሆኗ ይታወሳል። በዚያ የውድድር ዘመን በወንዶች ምድብ አብሯት ለመሸለም የበቃው አሜሪካዊው የአጭር ርቀት ሯጭ ታይሴን ጌይ ነበር፡፡ ከዓለም ኮከብ አትሌትነት ባሻገር አይ..ኤፍ በሚያዘጋጀው ዓመታዊ የሽልማት ስነስርዓት ሌሎች ክብሮችን ያገኙ ኢትዮጵያውያን የአትሌቲክስ ጀግኖችም አሉ፡፡

2014/15 የውድድር ዓመት በአትሌቲክስ ስኬታማ ጊዜን ያሳለፈችው አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በዓለማቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የዓመቱ ምርጥ አትሌት ለመሆን የበቃች የዘመናችን አትሌት ነች። ገንዘቤ ዲባባ ይህን ሽልማት ስታሸንፍ ከመሰረት ደፋር ቀጥላ ሁለተኛዋ ሴት ኢትዮጵያዊት አትሌት ነች። በወንዶች በኩል አሜሪካዊው አሽተን ኢተን የዓመቱ ምርጥ አትሌት በመሆን አብሯት ተሸላሚ ነበር።

ገንዘቤ ዲባባ በሩጫ ዘመኗ በዋናዎቹ የዓለም አቀፍ ውድድሮች በመካከለኛና ረጅም ርቀት ስድስት የወርቅ ሜዳልያዎች፤ አንድ የብርና አንድ የነሐስ ሜዳልያዎች መሰብሰብ በቻለችበት ወቅት ነበር ለዚህ ክብር የበቃችው። በተጨማሪም አራት የዓለምና ስድስት የአፍሪካ ክብረወሰኖችን በማስመዝገብ የበላይነቷን ባሳየችበት ወርቃማ ዘመኗ ነው ለዚህ ክብር መብቃት የቻለችው። በተለይ በ2015 በሞናኮ ካስመዘገበችው የ1500 ሜትር አዲስ የዓለም ክብረወሰን በኋላ በሩጫ ዘመኗ ያስመዘገበቻቸው የዓለም ክብረወሰኖች ብዛት አራት መድረሳቸው የአትሌቷን ዝና ከኮከብነት ሽልማቱ በዘለለ ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈ እንደነበር ይታወሳል።

ገንዘቤ በ1500 ሜትርና በ3ሺ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድሮች እንዲሁም በ2 ማይል ሩጫ የተመዘገቡት ሦስት የዓለም ክብረወሰኖች ሌላ አትሌት በድጋሚ ሊሰብር የሚችለው ቢያንስ ከ5 አመታት በኋላ እንደሚሆን በባለሙያዎች ሲገለፅም ቆይቷል። የገንዘቤ አራት የዓለም ክብረወሰኖች የሚከተሉት ሲሆኑ፤ በ1500 ሜትር መም 3:50.07 ፤ በ1500 ሜትር የቤት ውስጥ አትሌቲክስ 3:50.07 ፤ በ3ሺ ሜትር የቤት ውስጥ አትሌቲክስ 8:16.60 እንዲሁም በ5ሺ ሜትር የቤት ውስጥ አትሌቲክስ 14:18.86 በሆኑ ጊዜዎች የተመዘገቡ ናቸው፡፡ በ2015 እኤአ በ5ሺ ሜትር የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ፤ የዓለም የ5ሺ ሜትር የቤት ውስጥ ሩጫ ክብረወሰን ከማስመዝገቧም በላይ የዓለም ቻምፒዮና የብር ሜዳልያ አግኝታለች፡፡ በ1500 ሜትር የዓለም ሪከርድ አስመዝግባ ከዚያም በዓለም ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ ተቀዳጅታለች፡፡ ተመሳሳይ ስኬት በነበራት የ2014 የውድድር ዓመት ግን ከመጨረሻዎቹ ሦስት የዓመቱ ኮከብ አትሌቶች እጩዎች አንዷ ብትሆንም ሽልማቱን አላገኘችም ነበር። ሆኖም በተመሳሳይ የውድድር ዓመት በቻይና ሻንጋይ በሚካሄደው የላውረስ የዓመቱ ምርጥ ስፖርተኞች ሽልማት አሸናፊ በመሆን የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት እንደነበረች አይዘነጋም።

በዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ተሸላሚ በ1998 እኤአ ላይ ኃይሌ ገብረስላሴ ነበር፡፡ ኃይሌ በዚያን ወቅት በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ በ10ሺ ሜትር ባርሴሎና ላይ ከማስመዝገቡም በላይ በ10ሺ እና በ5ሺ የዓለም ክብረወሰኖችን በመያዝ ከፍተኛ የበላይነት ስለ ነበረው ኮከብ ሆኖ ለመመረጥ ብዙም አልተቸገረም፡፡ ከዚያ በኋላ በ2004 እኤአ ላይ ቀነኒሳ በቀለ ሁለተኛው የዓለም ኮከብ አትሌት ለመሆን በቃ፡፡ ቀነኒሳ በዚህ የውድድር ዘመን እስካሁን በእጁ የተያዙትን የ10ሺ እና የ5ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰኖችን አስመዝግቧል፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮናም በድርብ የወርቅ ሜዳልያዎች በማግኘትም የነገሰበት ዘመን ነበር፡፡

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ2005 እኤአ ላይም በረጅም ርቀት እና በዓለም አገር አቋራጭ ውድድሮች የበላይነቱን ቀጠለበት፡፡ ስለሆነም ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት የዓለም ኮከብ አትሌት ሆኖ ለመሸለም በቅቷል፡፡ ቀነኒሳ በዓለም ኮከብ አትሌትነት ሽልማቱን ለሁለት ጊዜ በመቀበሉ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ አድርጎታል፡፡ በሴቶች ምድብ ከቀነኒሳ በቀለ ጋር ሁለቱንም ተከታታይ ዓመታት የዓለም ኮከብ አትሌት ሆና ለመሸለም የበቃችው ራሽያዊቷ የምርኩዝ ዘላይ ዬሌና ኢዝንባዬቫ ነበረች፡፡ መሰረት ደፋር ከቀነኒሳ በኋላ ነበር በዓለም ኮከብ አትሌትነት ለመሸለም በመብቃት የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ ሴት አትሌት ለመሆን የቻለችው።

ከዓለም ኮከብ አትሌትነት ባሻገር አይ..ኤፍ በሚያዘጋጀው ዓመታዊ የሽልማት ስነስርዓት ሌሎች ክብሮችን ያገኙ ኢትዮጵያውያን የአትሌቲክስ ጀግኖችም አሉ፡፡ አሰልጣኝ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ብቸኛውን የአይኤኤኤፍ የህይወት ዘመን ስኬት ሽልማት ተቀብለዋል፡፡ በ2005 እና በ2008 እኤአ ላይ ደግሞ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የዓመቱ ምርጥ ብቃት ያሳየች አትሌት ተብላ ለሁለት ጊዜ ተሸልማለች፡፡

በዘንድሮው ሽልማት በወንዶች አሜሪካ፤ እንግሊዝና ደቡብ አፍሪካ ሁለት ሁለት እጩዎችን በማስመረጥ ቀዳሚ ሲሆኑ ኳታር፤ ፖላንድ፤ኬንያ፤ ጃማይካና ጀርመን አንዳንድ እጩዎችን ማስመረጥ የቻሉ አገራት ናቸው። በሴቶች ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ አስሩም እጩዎች የተለያዩ አገራት አትሌቶች ናቸው።

ሩሲያ ላይ ከአበረታች መድሃኒት ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ በተጣለው ቅጣት ምክንያት እራሷን ወክላ በዓለም ቻምፒዮናና በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ላይ በውድድር ዓመቱ አሸናፊ መሆን የቻለችው የከፍታ ዝላይ ተወዳዳሪ ማሪያ ላሲትስኬኒ በእጩዎቹ ዝርዝር ውስጥ ከአልማዝ አያና ቀጥሎ ስሟ ተፅፏል።

የለንደኑን የዓለም ቻምፒዮና ጨምሮ ለሁለተኛ ጊዜ የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ መሆን የቻለችው ግሪካዊቷ ምርኩዝ ዘላይ ካተሪና ስቴፋኒዲም ከእጩዎቹ መካከል መካተት ችላለች። በለንደኑ ቻምፒዮና በአምስት ሺ ሜትር አልማዝ አያናን በድንቅ ብቃት ማሸነፍ የቻለችው ኬንያዊቷ ሔለን ኦቢሪም የዳይመንድ ሊግ ስኬቷ ታክሎበት አንዷ እጩ ለመሆን በቅታለች። የዓለም ቻምፒዮኗና ለስድስተኛ ጊዜ የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ የሆነችው ክሮሺያዊቷ ዲስከስ ወርዋሪ ሳንድራ ፔርኮቪችም ከእጩዎቹ አንዷ ነች።

አውስትራሊያዊቷ የኦሊምፒክና የዓለም የመቶ ሜትር መሰናክል ቻምፒዮን ሳሊ ፒርሰን ከእጩዎቹ መካከል ስሟ የሰፈረ አትሌት ነች። ደቡብ አፍሪካዊቷ የመካከለኛ ርቀት ኮከብ አትሌት ካስተር ሲሜንያም ከስምንት መቶ ሜትር እስከ አንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ርቀቶች በውድድር ዓመቱ ባሳየችው ድንቅ ብቃት እጩ መሆን ችላለች። አሜሪካዊቷ ርዝመት ዘላይ ብሪትኒ ሪስና ቤልጂየማዊቷ ሁለገብ አትሌት ኔፊሳቱ ቲያም እንዲሁም ፖላንዳዊቷ መዶሻ ወርዋሪ አኒታ ቮዳርዛይክ ከአስሮቹ እጩዎች መካከል ይገኙበታል።

ባለፉት አስር ዓመታት ጃማይካዊው የአጭር ርቀት ንጉስ ዩሴን ቦልት የሌለበት የዓለም ምርጥ አትሌት እጩዎች ዝርዝር ማስታወስ ይከብዳል። ቦልት በለንደኑ ቻምፒዮና በድል ታጅቦ ራሱን ከውድድር ያገላል ተብሎ ቢጠበቅም ቻምፒዮናው ለእሱ መልካም እንዳልነበረ ይታወሳል። ይህም ከምርጦቹ አስር እጩዎች ዝርዝር መካከል እንዳይካተት አድርጎታል። በተመሳሳይ ለንደን ላይ የመቶ ሜትር ክብሩን ከቦልት የተቀበለው አሜሪካዊው ጀስቲን ጋትሊን አለመካተቱ ግን ብዙዎችን አስገርሟል።

ጋትሊን በቅርቡ በአበረታች መድሃኒት ተጠቃሚነት ከቅጣት መመለሱ ሳያስመርጠው እንደቀረ ይጠረጠራል። ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማሕበር ከዓመት በፊት በነበረው የምርጫ ሂደት አስቀድሞ በሰጠው ማሳሰቢያ ከእዚህ ቀደም አበረታች መድኃኒትን ተጠቅሞ ከመገኘት ጋር በተያያዘ የተቀጡ አትሌቶችን መምረጥ እንደማይቻልም ማሳወቁ አይዘነጋም።

አሜሪካዊው ስሉስ ዘላይ ክርስቲያን ቴይለር እጩዎቹ ውስጥ ሲካተት ኳታራዊው ከፍታ ዘላይ ሙታዝ ባርሺም እጩ መሆን ችሏል። እንግሊዛዊው የአስር ሺ ሜትርና የዳይመንድ ሊግ ቻምፒዮን ሞሐመድ ፋራህ በአምስት ሺ ሜትር ክብሩን ያስረከበበት ዓመት ቢሆንም እጩ መሆኑ ቀደም ብሎም የሚጠበቅ ነበር። የሦስት ጊዜ የዓለም ቻምፒዮኑ ፖላንዳዊው መዶሻ ወርዋሪ ፓውል ፋዴክ፤ አሜሪካዊው ምርኩዝ ዘላይ ሳም ኪንደሪክስ፤ ኬንያዊው የአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ሯጭ ኤሊጃ ማናጎይ፤ ደቡብ አፍሪካዊው የአጭር ርቀት አትሌት ሉቮ ማንዮንጋና የአገሩ ልጅ የአራት መቶ ሜትር የክብረወሰን ባለቤት ዋይድ ቫን ኒከርክ ከእጩዎቹ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል። የኦሊምፒክና የዓለም የመቶ አስር ሜትር መሰናክል ቻምፒዮኑ ጃማይካዊ ዩዜን ቦልት ባይኖርም ለጃማይካ ተስፋ ሆኗል። ጦር ወርዋሪው ጆሃንስ ቪተርም ከሞ ፋራህ ቀጥሎ እንግሊዝን እጩ ሆኖ የሚወክል አትሌት ነው።

በሁለቱም ፆታዎች አሸናፊ የሚሆኑ አንዳንድ አትሌቶች የሚመረጡት በሦስት መንገድ ይሆናል። የዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ምክር ቤት የሚሰጠው ድምፅ ሃምሳ በመቶ ነጥብ የሚኖረው ሲሆን፤ የዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች አባላት በኢሜል የሚሰጡት ድምፅ እንዲሁም የአትሌቲክስ አፍቃሪዎች በተለያዩ ዘመናዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰጡት ድምፅ ሃምሳ በመቶ ነጥብ የሚይዝ ይሆናል። በመጨረሻ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች በመጪው የፈረንጆች ወር በገባ በሁለተኛው ቀን ሞናኮ ላይ በሚካሄድ ስነ ስርዓት ይፋ የሚደረግ ይሆናል።

 

ቦጋለ አበበ

Published in ስፖርት

 

1990ዎቹ አካባቢ በመገናኛ ብዙኃን፣ በየትምህርት ቤቶችና ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ሁሉ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ አጀንዳ ሆኖ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ስለመተላለፊያ መንገዶችም ሆነ መከላከያውን በተመለከተ በብዙ አጋጣሚዎች ለህብረተሰቡ ግንዛቤው ይሰጥ ነበር፡፡ በትምህርት ቤቶች ውስጥ በስነ ጽሑፍና ድራማ ወጣቶች እርስበርስ ይማማሩ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እነዚህና መሰል አካሄዶች የቀነሱ ይመስላል፡፡

ወጣት ጌጥዬ ያለው እንደሚለው፤ ኤች.አይ .ቪ ኤድስ እንደተከሰተ ሰሞን የሚሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች ከፍተኛ ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡ ወጣቶች በሚንቀሳቀሱበት አጋጣሚ ሁሉ ስለበሽታው አስከፊነት በጥልቅ ሲወራ ይሰሙ ነበር፡፡ ይህን መስማታቸው ደግሞ ከወዲሁ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚያግዝ ነው፡፡ በትምህርት ቤት አካባቢ ይፈጠር የነበረው ግንዛቤ በወጣቱ ላይ ብቻ ሳይሆን የተማሪ ወላጆች እንኳን ያካትት ነበር። ሕብረተሰቡም መከላከል ላይ እንዲያተኩር አድርጎታል፡፡

ወጣት ጌጥዬ፣ በአሁኑ ወቅት ለኤች.አይ.ቪ ኤድስ የተሰጠው ትኩረት እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ ወጣቶች ስለ ቫይረሱ ምንም ግንዛቤ እንዳይኖ ራቸው ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው ይናገራል፡፡ በመገናኛ ብዙኃንም ሆነ በትምህርት ቤቶች አካባቢ ስለቫይረሱ ትምህርት መስጠት ከቀረ አሁን ላይ ያሉ ታዳጊዎች ስለመተላለፊያና መከላከያ መንገዶች እንኳን ላያውቁ ይችላሉም ይላል፡፡ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛነት በዚሁ ከቀጠለ እንኳን ታዳጊዎች በፊት ግንዛቤው የነበራቸው ራሱ ሊዘናጉ እንደሚችሉም ነው የሚናገረው፡፡

እንደ ወጣቱ አገላለጽ፤ ለመገናኛ ብዙኃንም ይሁን ለወጣቶች መዘናጋት እንደ ምክንያት የሚቆጥረው መሃል ላይ የሥርጭቱ መጠን መቀነስ ታይቶበት ስለነበር ነው፡፡ ይህ የሆነው ግን በ1990ዎቹ ይሰጠው የነበረው ትኩረት ከፍተኛ በመሆኑ ያመጣው ለውጥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህም መረዳት የሚቻለው በጉዳዩ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራ በሽታውን መቆጣጠር ስለመቻሉ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የቫይረሱ ሥርጭት እንደገና መስፋፋት ጀምሯል፤ ለመስፋፋቱ በምክንያትነት ሊጠቀስ የሚችለው መዘናጋት ነው። በተለይም በከተሞች አካባቢ የወሲብ ንግድ መስፋፋቱ ደግሞ ችግሩን አባብሶታል፡፡ በየመንገዱ ዳር ለወሲብ ንግድ የሚቆሙ ሴቶች ሲታዩ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ነገር በጭራሽ የሌለ በማስመሰሉ መዘናጋትን ፈጥሯል፡፡

በመገናኛ ብዙኃን አካባቢም እየታየ ያለው መዘናጋት እንደሆነ ወጣቱ ያመለክታል። ጉዳዩን አስመልክተው ሽፋን ካለመስጠት ባለፈ የአቀራረብም ችግር እንዳለ ነው የሚገልጸው፡፡ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ስርጭት በዕድሜ ባይወሰንም በስፋት የሚታየው ግን ወጣቱ ላይ ስለሆነ የወጣቶችን ቀልብ በሚይዝ መልኩ አይቀርብም፡፡ ዘመኑን የተከተለና እያዝናና የሚያስተምር መሆን አለበት፡፡ ሁሌም በተለመደው መንገድ ብቻ ማቅረብ ወጣቱን ያሰለቸዋል፤ ስለ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ የሆነ ትምህርት ነክ አሊያም ምክር አዘል ማስታወቂያ በተለመደው መልክ የሚቀጥል ከሆነ ወጣቱ ማድመጡን ወይም ማንበቡን ሊተወው ይችላልና የማስተማሪያ መንገዱ ሊቀየር እንደሚገባው ነው ያብራራው። ማህበረሰቡ የዘነጋውን ጉዳይ መገናኛ ብዙኃን አጀንዳ ፈጥሮ መነጋገሪያ ማድረግ እንደሚችልም ይጠቅሳል፡፡

ሌላኛው ወጣት ተመስገን መለስ፣ የሚመረመረው ወጣት ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ እንጂ ባለው ነባራዊ ሁኔታ የቫይረሱ ሥርጭት ሊቀንስ እንደማይችል ይናገራል፡፡ ጭፈራ ቤቶችና በየቦታው የዝሙት ተዳዳሪ በበዛበት ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ቀንሷል ማለት እንደማይቻልም ያመለክታል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ወጣት ቢመረመር እውነታውን ማወቅ እንደሚቻል ነው የሚናገረው፡፡

እንደ ወጣት ተመስገን አባባል፤ መመርመር ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ ብዙ ወጣቶች ይገኝብኝ ይሆናል በሚል ሥጋት አይመረመሩም፤ ነገር ግን በዚህ ውስጥ ካለው ጭንቀት ይልቅ ራስን አውቆ ቫይረሱ በደም ውስጥ ቢኖር እንኳን ራስን የመንከባከብ ጥንቃቄ ለማድረግ ያስችላል፡፡ በዘፈቀደ ይኖርብኛል አይኖርብኝም ከማለት ይልቅ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ራስን ለመቆጣጠር ያመቻል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የምርመራ አስፈላጊነትን በተመለከተ የምክር አገልግሎትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች የተቀዛቀዙ በመሆናቸው መነሳሳትን አልፈጠረም፡፡ ካለፈው ይልቅ በአሁኑ ወቅት በተሻለ የግንዛቤ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ግን ሊዘነጋ አይገባም።

ወጣት ጌጥዬ እና ወጣት ተመስገን በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠሩ በኩል ሐሳባቸው ቢመሳሰልም በሽታውን አክብዶ በማየትና ባለማየት በኩል ግን ልዩነት ይታይባቸዋል። ኤች.አይ.ቪ ኤድስ እንደ ቀላል መታየቱና ቫይረሱ ያለበት ሰው እንደማንኛውም ሰው ይኖራል እያሉ መናገሩ ልክ እንዳልሆነ ነው ወጣት ጌጥየወ የሚያምነው፡፡ ጌጥዬ ለዚህ ሀሳቡ ሁለት ምክንያት አለው፡፡ አንደኛ ቫይረሱ ያለበት ሰው የሚኖረው እንደማንኛውም ሰው አይደለም፤ ማንኛውም ሰው ማድረግ ያለበትን ነገር አያደርግም፡፡ ሁለተኛ ቫይረሱን እንዲህ ማቃለሉ መዘናጋትን እየፈጠረ ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ የሚያድን መድሃኒት እስካልተገኘለት ድረስ ‹‹የዕድሜ ማራዘሚያ›› የሚባለው ነገር አያወጣም፤ ይህ አይነቱ አካሄድ ወጣቱን ወደ ማዘናጋት ውስጥ የሚከተው እንደሆነ ነው የሚናገረው።

እንደ ወጣቶቹ አስተያየት፤ በቫይረሱ ላይ ይሰጥ የነበረው ትኩረት ቀንሷል፡፡ የምክር አግልግሎትም ሆነ ምርምራ ባለመደረጉ እንጂ ቫይረሱ ቀንሶ ላይሆን ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡ እንዲያም ሆነ ግን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ጊዜያዊ የምርመራ ጣቢያዎችን መታየታቸው አልቀረም፡፡

በእርግጥ በእነዚህ የምርመራ ጣቢያዎች እየተሰራ ስላለው እንቅስቃሴ የኤድስ ሄልዝ ኬር ፋውንዴሽን የፕሪቬንሽን ፕሮግራም ማኔጀር አቶ ሄኖክ መለስን አዲስ ዘመን ጋዜጣ አነጋግሯቸዋል። እርሳቸውም በሰጡት መረጃ እንደተናገሩት፤ ፋውንዴሽኑ ተቀማጭነቱ አሜሪካ ሆኖ ነገር ግን በተለያዩ የዓለም አገራት ላይ ኤች.አይ.ቪ ኤዲስን ለመከላከል በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል፡፡ በኢትዮጵያም የምርመራና የምክር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፤ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ለተገኘባቸው ወገኖችም የህክምና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በዚህ ፋውንዴሽን አማካኝነት ባለፈው ዓመት ብቻ ከህዳር ወር ጀምሮ አንድ መቶ ሃያ ሺ ያህል ወጣቶች ተመርምረዋል፡፡ ቫይረሱ ለተገኘባቸዋው ወገኖችም ድጋፍ ተደርጓል፡፡

ባለፈው ዓመት ብቻ አንድ መቶ ሃያ ሺ ወጣት በመመርመሩም የመመርመር ባህሉ መኖሩን ነው አቶ ሄኖክ የሚናገሩት፡፡ ግንዛቤው በተሟላ መልኩ አለ ባይባልም ብዙ ወጣቶች ግን ይመረመራሉ፤ የምክር አገልግሎትም ይወስዳሉ፡፡ ካለው የወጣት ቁጥር አንጻር 120 ሺ ብዙ ነው ባይባልም ለውጥ እንዳለ ግን ያሳያል ነው የሚሉት፡፡

እንደ እርሳቸው አገላለጽ፤ ስለ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ይሰጥ የነበረው ትኩረት ቀንሷል፡፡ ይህ የሆነውም በባለድርሻ አካላት ጉዳዩ ቸል በመባሉ ነው፡፡ በመንግስት በኩል እንኳን እየተሰራበት አይደለም፡፡ መገናኛ ብዙኃን ቀደም ሲል ይሰሩበት የነበረውን ፕሮግራም እንኳን እየሰረዙ በሌላ ተክተውታል፡፡ የእነዚህ አካላት ትኩረት አለመስጠት ደግሞ ሕብረተሰቡን እንዲዘናጋ አድርጎታል፡፡ ቫይረሱ የጠፋ የሚመስላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች አይታጡም፤ ነገር ግን በመገናኛ ብዙኃን ዝም ተባለ ማለት ቫይረሱ ጠፍቶ ነው ማለት አይደለም፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ይደረግ በነበረው ቁጥጥር በመድሃኒትና በመከላከል በእርግጥም ለውጥ ታይቶ ነበር፡፡ በዚህም ብዙ ሞትን መቀነስ ተችሏል፤ በሚሰጠው መድሃኒትም አልጋ ላይ መዋልን ማዳን ተችሏል፡፡ መከላከሉም ሆነ ህክምናው ተጠናክሮ ካልቀጠለ ግን የታየው ለውጥ ይቀጥላል ማለት አይደለም፡፡

በሌላ በኩል ለኤች.አይ.ቪ ኤድስ የአንድ ሰሞን ርብርብ መሆን እንደ ምክንያት የሚጠቅሱት መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ብዙ ፈንድ ይገኝ ስለነበር ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ ይደረግ የነበረ እንቅስቃሴ ሁሉ ገንዘብ ያስገኝ ስለነበር ብዙ ተሳታፊ ነበር የሚገኘው፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚመደቡ ገንዘቦች ቀንሰዋል፤ ገንዘቡ ሲቀንስ እንቅስቃሴውም አብሮ ቀነሰ፡፡ ጉዳዩ አሳሳቢ ሆኖ ሳለ ከገንዘብ ጥቅም ጋር ከተያያዘ ችግሩ አሁንም አሳሳቢ ይሆናል ሲሉ ነው የሚያብራሩት፡፡

በተለይም ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ በመንግስት በኩል ትኩረት እንዳልተሰጠ ነው አቶ ሄኖክ የሚናገሩት፡፡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ርዳታ ቢያደርጉም በምን መልኩና የት አካባቢ መሆን እንዳለበት ክትትል ሊደረግላቸው ይገባል ባይ ናቸው፡፡ ኤድስ ሄልዝ ኬር ፋውንዴሽንም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እየተንቀሳቀሰ ይሰራል፡፡ በትምህርት ቤቶችና በፋብሪካዎች አካባቢ እየተንቀሳቀሰ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ላይ እየተፈጠረ ያለው መዘናጋት ሊበቃ ይገባል፡፡ በመገናኛ ብዙኃን ትኩረት አጣ ማለት ቫይረሱ ጠፋ ማለት አይደለም፡፡ በየትምህርት ቤቶችም ሆነ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ያለው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ሊቀጥል ግድ ይላል፡፡ ከውጭ የሚገኙ የገንዘብ ድጋፎች መቀነስ ነገሩን ሊያቀዛቅዝ አይገባም ሲሉ ይናገራሉ፡፡ የሕይወት ጉዳይ ከገንዘብ ጋር የሚለካ መሆን እንደሌለበትም ነው የሚያመለክቱት፡፡

 

ዋለልኝ አየለ

 

 

Published in ማህበራዊ
Thursday, 05 October 2017 18:16

ሥልጣን የተመኘሁበት ቀን

 

ከልባቸውም ይሁን ከአንገት በላይ ባይታወቅም ብዙ ሰዎች «ኸረ እኔ ሥልጣን አልፈልግም» ሲሉ ይሰማል (እኔ ግን አላምናቸውም)፡፡ ሥልጣን አለመፈለግ እንደ ጥሩ ነገር የታየው ደግሞ በተሳሳተ ግንዛቤ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ ይህ ሊሆን የቻለው አንዳንድ ባለሥልጣኖች በሚያሳዩት ተገቢ ያልሆነ ነገር ነው፡፡ በእነዚህ ሰዎች ምክንያት ለሥልጣን የተሰጠው ትርጉም ሕዝብን ማጭበርበር፣ ጉቦ መቀበልና መክበር፣ ሥልጣንን ተገን አድርጎ ፍላጎትን ማሟላት የሚል ነው፡፡ በመሰረቱ ግን ሥልጣን ማለት ይህ አልነበረም፡፡

ሥልጣን ማለት ሥልጡን ከሚለው ቃል ጋር እናገናኘው፡፡ ሥልጡን ማለት የሰለጠነ ነው፡፡ ሕዝቡን በጨዋነት የሚያገለግል፣ ሕዝብን በማገልገል ችግሩን የሚፈታ ነው፡፡ ሥልጣን አግባብ ያልሆኑ ነገሮች ሥርዓት እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚያስችል ወንበር የሚገኝበት ነው፡፡ ኸረ ማነው ለሥልጣን ትርጉም ሰጪ ያደረገኝ? አትፍረዱብኝ በአንድ የጉዞ ገጠመኝ ላይ ያየሁት ነገር ምኞቴን በድንገት ባለሀብት ከመሆን ባለስልጣን ወደ መሆን ቀይሮብኝ ነው (ምን ዋጋ አለው ሁለቱም ምኞት ነው)፡፡ እንደዚያ ቀኑ ባለሥልጣን መሆን ተመኝቼ አላውቅም፡፡ ባለሥልጣን ሲባል ደግሞ የግድ ሚኒስትር መሆን ብቻ አይደለም፡፡ የትኛውም ኃላፊነት ይሰጠኝ ብቻ ባለሥልጣን ልሁን ነው ያልኩት፡፡ ለማንኛውም ወደ ጉዳዩ፡፡

ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ከአንድ ገጠራማ አካባቢ ወደ አዲስ አበባ እየመጣን ነው፡፡ በአካባቢው በቂ የትራፊክ ፖሊሶች አሉ፡፡ ይሁንና በዚህ አካባቢ የሚሄዱትን መኪናዎች ብዙ ጊዜ ሳስተውላቸው የሚጭኑት ምንም ሳላጋንን ልክ እንደ አዲስ አበባ አንበሳ ባስ ሰው በሰው ላይ አነባብረው ነው፡፡ ችግሩ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ሁሌም የሚያስከፍሉት ከመደበኛው ታሪፍ በላይ፤ አንዳንዴም ከታሪፉ እጥፍ ነው፡፡

የእዚያን ዕለት ዋጋ እንኳን ብጠቅስ መደበኛው ዋጋ 96 ብር ሆኖ የተከፈለው አንድ መቶ ሃምሳ ብር ነው፡፡ ለምን እንደሆነ ጠይቀነው «ካልፈለጋችሁ ተውት፤ መደበኛው ታሪፍ 96 ብር ሲሆን፤ እኔ ግን የማስከፍላችሁ 150 ብር ነው» በማለት ሕገወጥነቱን በግልጽ ነገረን፡፡ ነገሩን ለትራፊክ ፖሊሶች ብንናገር ስቀውብን አሳፍረው እንደሚመልሱን የአካባቢው ሰዎች ስለነገሩን ወዴትም መሄድ አልፈለግንም፡፡ ለመቶ ምናምን ኪሎ ሜትር መንገድ 150 ብር ከፍለን ቲኬታችን ላይ 96 ብር ተብሎ ተጽፎ ተሰጠን፡፡ ጉዞ ተጀመረ፡፡

በብዙ ቦታዎች ላይ የይስሙላ የትራፊክ ፖሊሶች አስቆሙን፡፡ የትራፊክ ፖሊስ ባየ ቁጥር ተጓዡ ሁሉ ይበሳጫል፡፡ ምንም ለማያደርጉት ጊዜ ማባከናቸው ነው ተጓዦችን የሚያበሳጫቸው፡፡ በር ላይ በተገጠገጡት ሰዎች የተነሳ ወደኋላ ማየት አይችልም፡፡ ከበሩ ላይ ጀምሮ በቆሙ ሰዎች የመኪናው መስኮትም ሆነ መጋራጃ አይታይም፡፡ በጣም ግርም ያለኝ ነገር እንደዚያ ሆኖ እያየው ዝም ብሎ የሚወርድ ከሆነ የተጓዡንስ ሆነ የራሱን ጊዜ ለምን ያቃጥላል?

እንግዲህ ሥልጣን የተመኘሁበት ጉዳይ ያለው እዚህ ጋ ነው (የእስካሁኑ ሥልጣን የጠላሁበት ነበር)፡፡ እንደተለመደው አንድ የትራፊክ ፖሊስ አስቆመና ገባ፡፡ መንገደኛውም እንደተለመደው አይቶ የሚመለስ መስሎት ጊዜውን ላለማባከን መመለሱን በጉጉት ይጠብቃል፡፡ ሰውየው ግን የዋዛ አልነበረም፡፡ እዚህ ላይ ሰውየውን ያደነቅኩት ሾፌሩን ስለቀጣው እንዳይመ ስላችሁ፡፡ እኔን ያስቀናኝ ለምርመራ የተጠቀመው ጥበብ ነው፡፡ ከልብ ከሰሩ ለካ ምንም ነገር አምልጦ አይቀርም፡፡

ገና ወደ መኪናው በር እንደገባ ወደ ኋላ ሲያይ ሰው በሰው ላይ ተነባብሮ ነው የተቀመጠው፡፡ የግርምት ፈገግታ ፈገግ አለ፡፡ ምንም ጭቅጭቅና ግርግር ሳይፈጥር፣ ለመቅጣት የቆረጠ ሳይመስል፣ «ምነው ይህን ሁሉ ሰው» ሳይል፣ «እስኪ መንጃ ፈቃድህን» ብሎ ከሾፌሩ ላይ ተቀበለ፡፡ መንጃ ፈቃዱን ይዞ ወደ ኋላ ሄደ፡፡ የሄደበትን ምክንያት ልብ በሉልኝ፡፡

ከፊት አካባቢ ያለነው ሰዎች ተማሪዎችና የተማርን የምንመስል ነን፡፡ እንግዲህ በልማዳችን መሰረት ሰውን በአለባበሱና በአነጋገሩ እንፈርጃለን፡፡ አንዳንዴም ልክ ነው፡፡ ከፊት ያለነው ከተማ ቀመስና ተማሪዎች እውነቱን እንደማን ነግረው ስለጠረጠረ ይመስለኛል ምንም ነገር መጠየቅ አልፈለገም፡፡ ወደኋላ ሄዶ አንድ ከገጠር የመጡ ሽማግሌን «አባባ ስንት ብር ነው የከፈሉትብሎ ጠየቃቸው፡፡ እርሳቸውም ቲኬታቸው ላይ እንኳን የተጻፈውን ስለማያውቁት «150 ብር» ሲሉ ሀቁን ተናገሩ፡፡ ትራፊክ ፖሊሱ ፈገግ አለና እዚያው አካባቢ ያሉ እንዲት አዛውንት ጠየቃቸው፡፡ እርሳቸውም «150 ብር» ሲሉ ተናገሩ፡፡

የትራፊክ ፖሊሱ አሁንም ምንም ጭቅጭቅና ወከባ ሳይፈጥር ረዳቱ ሰብስቦት ከነበረው ቲኬት አንድ ሁለቱን ተቀብሎ አየው፡፡ 96 ብር ይላል፡፡ ቲኬቱን ለረዳቱ መልሶ፣ ሾፌሩን ሁለት አማራጭ ያለው አንድ ጥያቄ ብቻ ጠየቀው፡፡ «ብራቸውን ብትመልስ ወይስ የመንጃ ፈቃድህን ብትቀማ ይሻልሃልሲለው ሾፌሩም «ክሰሰኝ» ሲል መለሰ፡፡ «እሺ ና ውረድ» አለና የሆነ ወረቀት ጻፈና ሰጠው፡፡ በዚህ ወቅት አንዳንድ መንገደኞች «አሁን በብር ይደራደረዋል» የሚል ሀሜት ነገር ማነሳሳት ጀመሩ፡፡

ከመካከላችን አንዱ የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ባለሥልጣን ሰራተኛ ነበር፡፡ ከመኪናው ወረድ አለና ትራፊክ ፖሊሱ ሌሎች ባልደረባዎቹ ወደ ቆሙበት ሄደ፡፡ መታወቂያውን ካሳየ በኋላ «እስካሁን ብዙ የትራፊክ ፖሊሶች እያዩ አልፈውታል፤ እናንተ ላይ ግን የሚያስደስት ነገር አይተናል፤ ግን የተጠራጠሩም አሉና የሚያረጋግጡበት ነገር ብታሳዩዋቸው» ሲል ጠየቃቸው፡፡ የትራፊክ ፖሊሱ «ይህ ሾፌር ካልተቀጣ እኔን ጠይቁኝ» ብሎ ስልኩን ሰጠ፡፡ የመኪናውን ታርጋ ሰጠ፡፡ አዲስ አበባ ሾፌሩን የሚቀጡትን ሰዎች አድራሻ ሰጠ፡፡

እዚህ ላይ ከምንም በላይ የገረመኝ የትራፊክ ፖሊሱ ቆራጥነት ነው፡፡ እነማንን መጠየቅ እንዳለበት አውቋል፡፡ የተማረ የሚመስለው ሰው እውነቱን እንደማይነግረው ጠርጥሯል፡፡ አልዋሽም እኔን «ስንት ነው የከፈልከውብሎ ቢጠይቀኝ ቲኬቱ ላይ ያለውን 96 ብር ብዬ ነበር የምመልሰው፡፡ ሰውየው ግን ሥራውን የሚሰራው ከልቡ ነው፡፡ እንደ ሌሎች የትራፊክ ፖሊሶች አይቶ ባይመለስ እንኳን ለማስመሰል ብዙ የውሸት ቁጣዎችን መጠቀም ይችል ነበር፡፡ ዝም ብሎ በደፈናው «ስንት ነው የከፈላችሁትቢል ኖሮ ማንም አይናገርም ነበር፡፡

እንግዲህ ሥልጣን የተመኘሁት ይህን የትራፊክ ፖሊስ አይቼ ነው፡፡ ከመንገደኞች ሁሉ ብዙ አድናቆት ወረደለት፡፡ በተለይ የተጠቀመው ዘዴ ለሕዝብ ማገልገል ከልብ እንደሆነ የሚያሳይ ነበር፡፡ በእንዲህ አይነት ሥልጣን ሰዎችን ከሕገ ወጥ ዝርፊያ ማዳን ይቻላል፡፡ የሰውን ልጅ ሕይወት መታደግ ይቻላል፡፡ ታዲያ እንዲህ አይነት ሥልጣን አያስመኝም ?

 

ዋለልኝ አየለ

Published in መዝናኛ

የደራ ወረዳ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኝ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ 220 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የወረዳው ከተማ ጉንደ መስቀል ይባላል። ወረዳው በሰሜን ደቡብ ወሎ፣ በምስራቅ መርሐ ቤቴ፣ በምዕራብ ምስራቅ ጎጃም እንዲሁም በደቡብ ኤጀርሳ ጎሮ እና ደገም ወረዳ ያዋስኑታል፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም መስመር በሚወስደው መንገድ ገንደ ሼኖ ላይ በመገንጠል ወደ ሰሜን አቅጣጫ እስከ ጉንደ መስቀል የሚያቀናው 86 ኪሎ ሜትር መንገድ አስቸጋሪ በመሆኑ ነዋሪዎች በተለያየ ጊዜ ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡ ከመንገድ በተጨማሪ የመብራት አገልግሎትም የተሟላ አይደለም፡፡

በደራ ወረዳ ውስጥ የሚታዩ የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያታቸው ምን እንደሆነና ችግሮችን ለመፍታት እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ እንዲሁም በወጣቶች ተጠቃሚነት ዙሪያ ስላለው ጉዳይ የወረዳውን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳምጠው ዘውዴን አዲስ ዘመን ጋዜጣ አነጋግሯቸዋል።

አዲስ ዘመን፦ በወረዳዋ የመሰረተ ልማት ዝርጋታው አለመሟላቱንና የመልካም አስተዳደር እጦት መኖሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ፤ ምክንያቱ ምን ይሆን?

አቶ ዳምጠው፦ በወረዳው ውስጥ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ በሚገባው ደረጃ አልተስፋፋም። ይህ የቅሬታ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። የመንገድ ጥያቄ አንዱ ነው፡፡ ከገንደ ሼኖ ላይ በመገንጠል ወደ ሰሜን አቅጣጫ እስከ ጉንደ መስቀል የሚወስደው ሰማንያ ስድስት ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ በአሁኑ ወቅት ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም፡፡ ይህ መንገድ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በአስፓልት ይሰራል ተብሎ እቅድ ተይዞ ሕዝብም ተወያይቶበታል፡፡ እንደ ክልልና ፌዴራል መንግስት መሰራት ያለባቸውን ነገሮች ለማከናወን በ2009 እና 2010 እቅድ ተይዟል፡፡ ሆኖም ግን በእቅድና አፈጻጸም ውስጥ ያየናቸው ችግሮች አሉ፡፡ ይኸውም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ውይይት አለማካሄዳቸው ለመንገዱ መዘግየት እንደ ምክንያት እየተጠቀሰ ነው። አሁን ጉዳዩ ያለው በፌዴራል መንግስት ነው፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለፌዴራል ደብዳቤ ጽፏል፡፡

ይሁንና የፌዴራል መንግስት ምንም ምላሽ አልሰጠም፡፡ በዚህም ምክንያት በወረዳዋ ትልቁና ዋና የሚባለው የመንገድ ችግር እስካሁን አልተ ፈታም፡፡ ከአዲስ አበባ በጎጃም መስመር የሚመጣው መንገድ ከገንደ ሼኖ ጀምሮ እስከ ደራ ወረዳ ድረስ አስቸጋሪ ነው፡፡ መንገዱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ነው ለሃያ ዓመታት አገልግሎት እየሰጠ ያለው፡፡ በአግባቡ ጥገና እንኳን አልተካሄደለትም፡፡

በእዚህ መንገድ ላይ ያለው የትራፊክ ፍሰት ከፍተኛ ነው፡፡ በቀን ውስጥ ከ350 በላይ መኪኖች ይመላለሱበታል፡፡ የአካባቢው መልክዓ ምድርም ወጣ ገባ በመሆኑ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህን በተመለከተ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው በማሰብ ጥያቄያችንን ያላማቋረጥ በማቅረብ ላይ እንገኛለን፡፡

ከመንገዱ ጋር ተያይዞ ሌላው የሚነሳው ነገር ተገቢው ጥገና ያለመደረጉ ነው፡፡ መንገዱ ለረጅም አመታት ተገቢው ጥገና አልተደ ረገለትም፡፡ አስቸጋሪ ከመሆኑ የተነሳ ጠዋት አሥራ ሁለት ሰዓት ከአዲስ አበባ የወጣ አንድ መኪና 220 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ደራ ወረዳ ለመድረስ አሥር ሰዓት ይወስድ በታል፤ ይህም የሚሳካው ዝናብ ካልዘነበ ብቻ ነው፡፡ ዝናብ ከዘነበ ደግሞ እዚያው ውሎ እዚያው የሚያድርበት አጋጣሚም አለ፡፡ ለዚህም ችግር መፍትሄ እንዲበጅለት በየጊዜው እየጠየቅን እንገኛለን፡፡

ስለዚህ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ችግር ባልተፈታበት ሁኔታ የመልካም አስተዳደር ችግርም መኖሩ የማይቀር ነው፡፡ መልካም አስተዳደር እንዲኖር የሕዝብ ተጠቃሚነት መረጋገጥ አለበት፡፡ ከተሰራበት ጊዜ ጀምሮ ምንም የደረጃ ዕድገት አላገኘም፡፡ ይሄ ደግሞ ከፍተኛ ችግር ስለሆነ የመንግስትን ትኩረት ይፈልጋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ጉዳዩ ያለው በፌዴራል መንግስት እጅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ስለዚህ ችግሩ የፌዴራል መንግስት ነው ማለት ነው?

አቶ ዳምጠው፡- የመንገዱ የዲዛይን ጥናት ሥራ ተጠናቋል፡፡ በ2007/2008 .ም የፌዴራል መንግስት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰጠው እውቅና ጥናቱ ተጠናቆ ተሰንዷል፡፡ በዚህም መሰረት በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ይካተታል ብለን ነበር የጠበቅነው፤ ዳሩ ግን አልተካተተም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የክልሉም ሆነ የፌዴራሉ መንግስት ድርሻ የጎላ አለመሆን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የፌዴራል መንግስት የሚለው ክልሉ ሊሰራልኝ ይገባል ብሎ ጥያቄ አላቀረበልኝም ነው፡፡ የክልሉ መንግስት ግን ደረጃውን የጠበቀ አስፓልት እንዲሰራ ለፌዴራል መንገዶች ባለሥልጣን ደብዳቤ ጽፏል፡፡ የተጻፈው ደብዳቤ ግን ለፌዴራል ሥራ አስፈጻሚ አካላት አልቀረበም፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤትም ሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት አላደረጉበትም፡፡ ውይይት ሳይደረግበት ደግሞ የፌዴራል መንገዶች ባለሥልጣን መልስ ሊሰጠን አይችልም፡፡

የክልሉ መንግስት ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የገንደ ሼኖ ደራ ጉንደ መስቀል መንገድ በክልሉ በጀት የሚሰራ ስላልሆነ ከአቅሜ በላይ ነው ብሎ አሳውቋል፡፡ ግልባጭም ለሰሜን ሸዋ ዞን መንገዶች ባለሥልጣን ሰሜን ጥገና ክፍል ሰጥተዋል፤ ዞኑም ለእኛ ግልባጩን ሰጥቷል፡፡ እኛም ጥያቄያችንን አሁንም አልቆመም፡፡

ከጥገና ጋር ተያይዞ ያለውም ሲታይ ሁለት አይነት ጥገናዎች ናቸው የሚስተዋሉት፡፡ እነዚህም መደበኛ ጥገና እና አልፎ አልፎ የሚደረግ ጥገና ናቸው፡፡ ለእነዚህ የሚለቀቀው የበጀት መጠን በጣም አነስተኛ ነው፡፡ 86 ኪሎ ሜትር ለመጠገን ሁለት ሚሊዮን አካባቢ ነው የሚያዘው፡፡ በዚህ የሚጠገን መንገድ አጥጋቢ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ የበጀት እጥረትም አለ ማለት ነው፡፡

የመንገዱ ነገር በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ ምቹ ካለመሆኑ የተነሳም የሰው ልጅ ህይወት ለአደጋ በመጋለጥ ላይ ነው። በተጨማሪም ህብረተሰቡ ንብረቱን እያጣ ነው፤ ገንዘቡንም ያለአግባብ እያወጣ ነው፡፡ 86 ኪሎ ሜትር ለመጓዝ የሚያወጣው 160 ብር በመሆኑ ክፍያው ከፍ ያለ ነው። ይህን ክፍያ አግባብነት ያለው እንዲሆን ለማድረግ ከዞኑ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ ጥያቄዎች ደረጃቸውን ጠብቀው ምላሽ ያገኛሉ የሚል ግምት አለን፡፡ የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪም ጥያቄውን በበላይነት ተቀብሎ ለህዝቡ መልስ እንደሚሰጥ ቃል ገብተዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሥራው አለመጀመር ሌሎች ምክንያቶች ይኖራሉ?

አቶ ዳምጠው፡- በተሀድሶ ጉዞ የአመራር ሽግሽግ በመኖሩ አንዱ የያዘውን መርሃግብር ሌላው ላይሰራው ይችላል፡፡ ስራዎች ትኩረት ያለማግኘትና የመረሳት ሁኔታም ይታያል፡፡ የትኩረት አቅጣጫዎች ምን ላይ ናቸው የሚለውን ክልሉም በበላይነት በመመልከት ለመፍታት የአስፈፃሚው አካል ክፍተት እንዳለው ይታወቃል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ ውስጥ መብራት መቆራረጥ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴም እስከ ሦስትና አራት ቀን ድረስ እንደማይኖር ነዋሪዎች ይናገራሉ፤ መፍትሄ ሊገኝ ያልቻለበት ምክንያት ምን ይሆን?

አቶ ዳምጠው፡- በመብራት አቅርቦት በኩል ያለውን እንቅስቃሴ ስንመለከት መታየት ያለባቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ የመብራት አገልግሎት የሃይል ማሰራጫችን ያለው መርሐቤቴ ዓለም ከተማ ነው፡፡ ከዓለም ከተማ ጉንደ መስቀል ያለው ርቀት 72 ኪሎ ሜትር ነው፡፡ የማሰራጫ መስመሩ በዚህ ርቀት መካከል ለሚዳ ወረሞ እና ደራ ለሁለት ተከፍሎ በመሄድ የሚሰራ ነው፡፡

የመብራት ማስተላለፊያ መስመሩ ጥገና የሚፈልግ ነው፡፡ የሃይል ማከፋፈያ ሲኒዎች በፀሀይና በሙቀት እየቀለጡ ነው፡፡ የአገልግሎት ጊዜያቸውም ያለቀ ነው፡፡ እድሳት ይፈልጋሉ፤ ግን አልተደረ ገላቸውም፡፡ ፈጣን መልስ ለመስጠት የሰው ኃይል ከመገልገያ ቁሳቁስ ጋር መሟላት አለበት፡፡ እኛ አካባቢ ያለው ሰራተኛ ተነሳሽነት ያለውና ህዝባዊ አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ ሜዳ አካባቢ ያለው አገልግሎት ደግሞ በአንድ ባለሙያና በአንድ ሳተላይት ነው የሚሰራው፡፡ ብልሽት ሲያጋጥም የት አካባቢ እንደተከሰተ ለማወቅ የሚደረግ እንቅስቃሴ በቂ አይደለም፤ ለትራንስፖርትም አመቺ የለውም፡፡ ችግሩ ያለበትን ቦታ መፈለግ በራሱ አስቸጋሪ በመሆኑ በሰው ኃይል ማሟላት በኩል ርብርብ ያስፈልገዋል፡፡

ከዓለም ከተማ ጀምሮ ያለው የሰው ሃይል አናሳ ነው፡፡ አገልግሎቱና እየተሰራ ያለው ሥራ ህዝባዊ አይደለም፡፡ በተለይም ከነሐሴ ወር 2009 .ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ህዝቡ የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ነው ብለን አንናገርም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ይህን ችግር ለመቅረፍ ምን ጥረት አድርጋችኋል?

አቶ ዳምጠው፡- ችግሩን ለማስወገድ በተለይ ምስራቅ አዲስ አበባ ሪጅንና ዋናው ኤሌትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ ድረስ በመሄድ ለሪጅኑ አቅጣጫ እንዲሰጥ አድርገናል፡፡ ነገር ግን በአቅጣጫው መሰረት እየተተገበረ አይደለም፡፡ በተለይ ለምስራቅ አዲስ አበባ ሪጅን በተለያየ ጊዜ ብናሳውቀውም መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ችግሩን እንዲወገድ ውይይትም ለማድረግ ብንሞክርም የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረባቸው ሊሳካ አልቻለም፡፡ ለውጥ ለማምጣት እየሰራን ነው የሚል መልስ ቢሰጡንም ለህዝቡ የሚጠቅም ስራ እየተሰራ አይደለም፡፡ እኛም ለሚመለከተው አካል እያዳመጠን እንዳልሆነና የተንዛዛ ቢሮክራሲያዊ አሰራር እንዳለው አሳውቀናል፡፡ አሁንም እስከ መጨረሻው ጥረታችንን በመቀጠል መፍትሄ የሚገኝበትን መንገድ እንፈልጋለን፡፡

የመብራት አገልግሎት አሁን ከእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ በመሆኑ በአካባቢው ለሚገኘው ሆስፒታልም ችግር ሆኗል። በዚህም ምክንያት በአግባቡ አገልግሎት እንዳይሰጥ አድርጎታል፡፡ ኦፕራሲዮን የሚሰራው በመብራት ነው፡፡ ስራው እየተሰራ እያለ በመሃል መብራት ሲቆም የሰው ሕይወት ነው የሚጠፋው፡፡ ለሚመለከተው አካል በየጊዜው ጉዳዩን በማሳወቅ መመሪያ እየተሰጠበት ነው፤ ነገር ግን የሚሰጠው ምላሽ አጥጋቢ አይደለም፡፡ የምስራቅ አዲስ አበባ ሪጅን የሚሰጠን ምላሽ አጥጋቢ እንዳልሆነ ዛሬም ነገም በአጽንኦት የምንናገረው ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ባለፈው ዓመት ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ተመድቦ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉትን ወጣቶች ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ በደራ ወረዳስ ይህ እንቅስቃሴ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ዳምጠው፡- በወጣቶች የስራ ፈጠራ በኩል የተሰሩ ስራዎች አሉ፡፡ በመጣው ተዘዋዋሪ ፈንድ ከ120 በላይ ማህበራት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በአባላት ብዛት ደግሞ እስከ 2500 አባላት በከተማና በገጠር ባላቸው የስራ እንቅስቃሴ በቢዝነስ እቅድ ላይ በማተኮር ከግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በእርባታ፣ በከተማ ማኑፋክቸሪንግ አገልግሎት እንዲሁም በገጠርና በከተማ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ነገር ግን በተዘዋዋሪ ፈንዱ ላይ የተበጀተልን በጀት በቂ አይደለም፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የተመደበው በጀት ከፍ ያለ ቢሆንም የመጣልን ግን አነስተኛ ነው፡፡ ችግሩ እንደ ሀገርም የታወቀ ስለሆነ የቀረውን በዚህ ዓመት ይሸፈናል የሚል ግምት አለን፡፡

እንደ ወረዳችን ወጣቱን ወደ ስራ ከማስገባት አኳያ የሚመጣውን ተዘዋዋሪ ፈንድ ብቻ ሳንጠብቅ ካለን የማህበረሰብ አቀፍ ስራዎች ለማግኘት የታሰበውን ገንዘብ ወደ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ወደ ብድር አገልግሎት በማስገባት እስከ ሁለት ሚሊየን ብር አካባቢ ብድር እንዲመቻች ሰጥተናል፡፡ በመደራጀት እውቅና የተሰጣቸው ወጣቶች አሁንም የገንዘብ ድጋፍ እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በወረዳው ውስጥ በተለይም በገጠር አካባቢዎች ደም መመለስ የሚባለው ልማድ አሁንም የብዙዎችን ሕይወት እያጠፋ ነው፡፡ ይህን ለማስቀረት ምን ተሰርቷል?

አቶ ዳምጠው፡- በፀጥታና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ህብረተሰቡን በዋናነት ያካተተ የንቅናቄ መድረክ ተፈጥሮ ለመስራት ብዙ ጥረት ተደርጓል፡፡ በተለይ በወረዳው ሰላምና ፀጥታ ዙሪያ በርካታ መድረኮች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ መድረኮች ተካሂደዋል፡፡ በዚህም የመጡ ለውጦች አሉ፡፡ በአካባቢው ግድያ የሚበዛው በተለምዶ ደም የሚባል ልማድ በመኖሩ ነው፡፡ ይህ ዘመድ ከዘመዱ ጋር የሚገዳደልበት ልማድ እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ የዜጎች ህይወታቸው ያለ አግባብ እያለፈ ነው፡፡ በዚህ ልማድ አምራች ዜጎችን እያጣን ነው፡፡

በበቀል ሰው የሚገድሉ ግለሰቦች የህግ የበላይነትን ከመቀበል ይልቅ ወደ ጫካ የመግባት፣ የሚኖሩበትን አካባቢ ወደ ሌላ በመቀየር የሟች ቤተሰብ ያለበትን በማደንና በመበቀል ችግሩን ቀጠይነት እንዲኖረው ያደርጋሉ፡፡ ይህ አስፈላጊ ባለመኖኑ ሁሉም ሰው ለህግ የበላይነት ሊገዛ ይገባል፡፡ ደረጃ በደረጃ ያለው አስፈፃሚ አካል ከህዝቡ ጋር በመነጋገር የመጡ ለውጦች አሉ፡፡

ነገር ግን አሁንም ግድያ እንዲቀር ከማድረግ ጋር ተያይዞ ባለፈው የበጋ ወቅት ላይ የተጀመሩ ስራዎች በመልካም ሂደት ላይ ናቸው፡፡ በክረምቱ ወራት በብቀላ የተነሳ የሞተ ሰው የለም፡፡ የሚነሱ ጉዳዮችን በጊዜ እርምጃ በመውሰድ ህብረተሰቡ በሰላም እርስ በርስ እንዲኖር ህዝቡም አምኖበት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

ጉንደ መስቀል ከተማን በተመለከተ አሁንም ክፍተቶች አሉ፡፡ የፀጥታ ሁኔታ የሚያደፈርሱና ከፍተኛ ዝርፊያ የሚፈጽሙ መኖራቸው ይታወ ቃል፡፡ ከህብረተሰቡ በሚመጣ ጥቆማ መሰረት በመለየት እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት ላይ ነው ያለነው፡፡ በዚህ በኩልም ከአስፈፃሚ አካላት ከፖሊስ ዓላማ አንፃር ህዝብን በማገልግል በኩል ክፍተቶች አሉ፡፡ በፖሊስ በኩል የአካባቢውን ሰላም ለመቆጣጠር በስራ በሚሰማሩበት ወቅት በቁርጠኛነት ሀላፊነትን በመወጣት በኩል ክፍተት ይታያል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በደም መመላለስ ልማድ ውስጥ ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውር ይኖራል፡፡ ይህን ለማስቀረት ምን ተሰርቷል?

አቶ ዳምጠው፡- እንደ ክልላችን የመሳሪያ ምዝገባ አልታገደም፡፡ ከዚያ በፊት በነበረው አሰራር ውስጥ በነበሩ ክፍተቶች ምዝገባ ያላገኙና የህገወጥ መሳሪያ ዝውውሮች ይስተዋሉ ነበር፡፡ አሰሳ በማድረግ 11 መሳሪያዎች ተይዘዋል፡፡ ሆኖም ግን ከቁጥጥርም አልፈው የሚያመልጡ አሉ፡፡ መሳሪያዎችን ለመያዝ ከሕብረተሰቡ ጥቆማ እናገኛለን፡፡ ከህብረተሰቡና ከአስፈጻሚ አካላት ጋር በመሆን አሁንም ርብርብ ይደረጋል፡፡ መሳሪያው ፈቃድ ስለሚያስፈልገው ከክልል ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር መፍትሄ የሚያገኝ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በተለያዩ አካባቢዎች ይገኛል፤ ይህን ለማጣራት ምን ተሰርቷል ?

አቶ ዳምጠው፡- የመንግስት ሰራተኞች በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያለ አግባብ እየተጠቀሙ መሆኑ ስለ ተረጋገጠ ራሳቸውን እንዲያጋልጡ እድል ተሰጥቷቸው በአቅማቸው መሰረት እንዲሰሩ ተደርጓል፡፡ በወረዳችን ራሳቸውን ያጋለጡ የመንግስት ሰራተኛ 30 ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎች ራሳቸውን ያላጋለጡም ይኖሩ ይሆናል፡፡ እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን እንዲያጋልጡ የተሰጣቸው ጊዜ አልፏል፡፡ አሁን የሚሰራው የኮሚቴ ሥራ ነው፡፡ ይህንን ለማጋለጥ የተቋቋመ ኮሚቴ የሀሰት ሰነዶችን ለማጋለጥ በሰባት ሰዎች ተዋቅሮ እየሰራ ነው፡፡ ይህም በቅርቡ ሥራውን ይጀምራል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ህዝቡ ከአመራሩ ጎን በመቆም ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችለው ትብብር ምን ይመስላል?

አቶ ዳምጠው፡- የደራ ወረዳ ህዝብ ለልማት ሰላምና ዴሞክራሲ ዘብ የቆመ ነው፡፡ ይህንን ልማት ወዳድና ሰላም ፈላጊ የሆነ ህዝብ አንጾ ለመሄድ በመንግስት አስፈፃሚ ሆነው የተሾሙ የትኛውም አስፈፃሚ አካላት እኔንም ጨምሮ ፈጣን መልስ መስጠት ላይ የሚወጣው ድርሻ አነስተኛ ነው፡፡ ስለሆነም ፈጣን ምላሽ የሚሹ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታትና መረባረብ ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ !

አቶ ዳምጠው፡- እኔም አመሰግናለሁ !

 

ዋለልኝ አየለ

Published in ፖለቲካ

 

ከአስራ አምስት ዓመት በፊት የእንግሊዙ ዕለታዊ ጋዜጣ ዘ ጋርዲያን ያስነበበው ዘገባ የአንድን ኩባንያ የቀውስ ገመና አደባባይ ያዋለ ነበር፡፡ በወቅቱ ስያሜ ‹‹ወርልድኮም›› የተሰኘው የአሜሪካ የቴሌኮም ኩባንያ የውስጥ ኦዲቱን በአግባቡ ባለማጥራቱ ‹‹በአካውንቴ አለ›› ሲል የተማመነው ከፍተኛ ገንዘብ የውሃ ሽታ ሆኖበታል፡፡ የኩባንያው የበዛ ኪሳራ ምክንያቱ የኩባንያው ሒሳብ አጣሪዎች ‹‹በካዝና አለ›› ያሉት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በትክክለኛ መረጃ ላይ አለመመስረቱ ነበር፡፡ ስህተቱን ተከትሎም ከ30ሺ የሚልቁ የኩባንያው ሰራተኞች ከስራቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ኩባንያውም ለ180 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ተዳርጓል፡፡

የኩባንያውን የከረመ ታሪክ ለመንደርደር ያህል በግርድፉ አስታወስን እንጂ በዓለም ምጣኔ ሀብት የአንበሳ ድርሻ ያላቸው ጎምቱ ኩባንያዎች እንዲህ ባለው አጋጣሚ ክፉኛ ተናግተዋል፡፡ በተለይም ከፈረንጆቹ ሁለተኛው ሚሊኒየም መባቻ አንስቶ ባሉት አስር ተከታታይ ዓመታት ከአስር የማያንሱ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች በተመሳሳይ ስህተት ለተመሳሳይ ‹‹ቅሌት›› ተዳርገዋል፡፡ የኃይል አገልግሎት፣ የንግድ፣ የፀጥታና ደህንነት፣ የጤና መድህን፣ የገንዘብ አበዳሪ ተቋማት፣ የኢንሹራንስ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በመዘዙ የኪሳራ ጠረን ያወዳቸው ኩባንያዎች ነበሩ፡፡

በእርግጥ የኩባንያዎቹ ኪሳራ ምክንያት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከግለሰቦች ብቃት ጋር ግንኙነት ቢኖረውም ከሙያ አንጻር ዘርፉ ምን ያህል ጥንቃቄ እንደሚፈልግ በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡ የአንድ አገር ምጣኔ ሀብት እያደገና የውጪ ኩባንያዎችን በኢንቨስትመንት የመሳብ አቅሙ እየተጠናከረ በመጣ ቁጥር የሂሳብ ሙያ ብቃትና ጥንቃቄም በዚያው መጠን ማደግ ይገባዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት በኋላ በተከታታይ እያስመዘገበች ካለችው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት አንፃር በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘርፉን የማሳደግ ግዴታ ውስጥ ከሚያስገቧት አሰራሮች መካከል ጥራት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ይጠቀሳል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር አብርሐም ተከስተ፤ በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ አንድ አገር ኢንቨስትመንት ለመጋበዝ መወዳደሪያ ከሚሆኑ ስልቶች መካከል ጥራት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ አንዱ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ «የአገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ ነው፤ የኢኮኖሚ ዘርፎቹም ዘመናዊ ናቸው፤ ዓለም ወደ እኛ እየመጣ ነው፤ ነገ ከነገ ወዲያ እኛም በንግድና ሌሎች ዘርፎች ወደ ዓለም እንወጣለን» የሚሉት ዶክተር አብርሐም፤ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገች እንደመምጣቷ የፋይናንስ ስርዓቷን በዓለም አቀፍ መመዘኛ ስልት መቃኘት እንደሚገባት ይገልጻሉ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዘርፍ ከምንም በላይ በባለሀብቶች ላይ የኢንቨስትመንት መተማመን መፍጠር ወሳኝ ነው፡፡

መንግስት ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ሥርዓት በመዘርጋትና የተመቸ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር ይሰራል፡፡ አላማውም በተጠናከረ የሂሳብ አያያዝ ኢንቨስትመንትን በማበረታታት የኢኮኖሚ ዕድገቱን መደገፍ፣ ማበረታታት እና ማረጋጋት ነው፡፡ ይሄን ሚናውን በመገንዘብም በሀገር ውስጥ በሚገኙ በግል፣ በመንግስት እና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ ተፈፃሚ የሚሆን ‹‹የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ›› አዋጅ 847/2006 ማውጣቱ ይታወቃል፡፡

አዋጁን ለማስፈጸምም «የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ» በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 332/2007 አቋቁሟል፡፡ የቦርዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጋሼ የማነ እንደሚሉት፤ አዋጁ የሚመለከተው የአካውንቲንግ እና ኦዲቲንግ ሙያን ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁኑም ዘርፉ የአገሪቱን ዘላቂ ልማትና እድገት ስለማረጋገጥ ጭምር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ አይነት ጥራት ያላቸው የፋይናንስ መረጃዎች አግባብ ባለው አካል ቁጥጥር ከተደረገባቸው እንደ አገር የሕዝብ እምነት ያድጋል፤ ኢንቨስትመንት ይበረታታል እንዲሁም የብድር አገልግሎቶች ይቀላጠፋሉ፡፡

ነገር ግን ይሄ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የተቋማትን የፋይናንስ ሪፖርት በወጥነት የሚተገብር ደረጃ (ስታንዳርድ) እንዳልነበር አቶ ጋሼ ይገልጻሉ፡፡ በዚህም የሒሳብና የኦዲት ስራዎችን የሚያከናውኑ ባለሙያዎች ምን ማሟላት እንደሚጠበቅባቸውና አቅማቸውን እንዴት መገንባት እንደሚገባቸው የሚያመላ ክታቸው ባለቤት አልነበራቸውም፡፡ በመሆኑም አዋጁ ሲዘጋጅ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚመራና የሕዝብ ጥቅምን የሚያስጠብቅ የሒሳብ አያያዝና የኦዲት ስርዓት እንዲፈጠር ለማድረግ ነው፡፡

የሪፖርት አቅራቢ አካላትን መመዝገብ፣ የሕዝብ ጥቅም ያለባቸውን ተቋማት ለይቶ ማወቅ፣ አነስተኛና መካከለኛ የሚባሉት ተቋማት የትኞቹ ናቸው? የትኞቹስ በአዋጁ ወሰን ስር ይካተታሉ? የሚለውን መለየትና ሌሎች ተግባራትን በማከናወን ስራ መጀመራቸውን አቶ ጋሼ ይጠቅሳሉ፡፡ ነገር ግን አገሪቱ በምትከተለው የፌደራል ስርዓት ክልሎች የራሳቸውን ሕግና አዋጅ የማውጣት ስልጣን በሕገመንግስቱ ስለተሰጣቸው አዋጁ በፌደራል ደረጃ ሲዘጋጅ ‹‹የክልሎችን ስልጣን ተጋፍቷል›› የሚል ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡

በያዝነው ወር አጋማሽ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መሰብሰቢያ አዳራሽ የሕግ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት በተደረገ ወቅት የተገኙት የትግራይ ክልል ዋና ኦዲተር ዶክተር ረዳዒ በርሄ፤ የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት 230/2005 ያወጣው አዋጅ መኖሩን ይገልጻሉ፡፡ በዚህ አዋጅ መሰረት በክልሉ ለሚገኙ የግል የሒሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች ክልሉ ፈቃድ የመስጠት፣ የሒሳብ ስርዓት የመመርመር እና ፈቃድ እንዲሰርዝ የማድረግ ስልጣን በክልሉ ምክር ቤት ተሰጥቶታል፡፡

ነገር ግን አዋጁ አገልግሎት ላይ ባለበት ሁኔታ በፌደራል ደረጃ «የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ» መቋቋም በአሰራሩ ላይ ክፍተት የሚፈጥር ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ይሄን በተመለከተ ክልሉ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ቅሬታ ማቅረቡን የሚያብራሩት ዶክተር ረዳዒ፤ በቅሬታው መሰረት አዋጁን የማሻሻል ስራ ተጀምሯል፡፡

አዋጁን በተመለከተ ከክልሎች ስልጣን ባሻገር ለቅሬታ መነሻና ምክንያት የሚሆኑት ክፍሎች የትኞቹ ናቸው? የቦርዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጋሽ፤ በቀደመው አሰራር አዋጁ በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ወደ ሒሳብ ስራ የሚገቡ አካላትን የሚወስን፣ ፈቃድ የሚሰጥ፣ የሚያድስና የሚቆጣጠር እንዲሁም የሕግ የማስከበር ስራ የሚከናወነው ሙሉ በሙሉ ቦርዱ እንዲሆን ያደርግ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ይሁንና በአዋጁ ማሻሻያ ግን የተጠቀሱትን ስራዎች ቦርዱ ብቻ ሳይሆን በየክልሎቹ የሚሰየም አካል ደረጃውን ጠብቆ ሊሰራበት የሚችል መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የአዋጅ ማሻሻያ ስራው ከተጀመረ በኋላ «የክልላችን ጥያቄ በተወሰነ ደረጃ መመለስ ጀምሯል» ያሉት የትግራይ ክልል ዋና ኦዲተር ዶክተር ረዳዒ፤ አሁን ግን የሚቀሩ ስራዎች መኖራቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ይቀራል ያሉት ስራም፤ አሁንም በፌደራል ደረጃ የሚወጣው አዋጅ ክልሎች ለሚያወጡት ስልጣን ዋስትና እንደማይሆን ስጋት አላቸው፡፡ በውይይቱም «ክልሎች የፌደራሉን አዋጅ መነሻ በማድረግ የራሳቸውን አዋጅ እንዲያወጡ ማድረግ ይገባል» የሚል ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ በፌደራልና በክልሎች መካከል ያለውን ሁኔታ በተመለከተ «ሁላችንም የምንሰራው ለአንድ አገርና ሕዝብ ነው» የሚሉት ዶክተር ረዳዒ፤ የሕዝብን ጥቅም ማዕከል ባደረገ መልኩ የሚሻሻለው አዋጅ ፍላጎቶችን ያገናዘበ ሊሆን እንደሚገባ ያሰምሩበታል፡፡

አንዳንድ ክልሎች አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ቀድሞ መሰራት የሚገባቸው ስራዎች ባለመከናወናቸው አሁን ላይ መጓተት መፈጠሩን ያነሳሉ፡፡ በተለይም እንዲህ አይነት ሕጎች ሲዘጋጁ በተናጠል ሳይሆን ክልሎችን ማዕከል ባደረገ መልኩ መዘጋጀት ይገባዋል በማለት፡፡ አዋጁ ከወጣ ሁለት ዓመት ቢሆነውም በአተገባበር ላይ ችግር የገጠመው ቀድሞ የጋራ መግባባት ስላልተፈጠረበት መሆኑንም ያምናሉ፡፡ «በዚህ አዋጅ ዙሪያ በክልላችን ምንም የተሰራ ስራ የለም» የሚሉት አቶ ረዳዒ፤ ነገር ግን ከክልሎች ጋር በቂ ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልግ ነበር፡፡

የአማራ ክልል ምክትል ዋና ኦዲተር አቶ ስመኝ ካሴ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሂሳብ አያያዝና የኦዲት ደረጃዎች (ስታንዳርድ) ቢኖርም እንደ ኢትዮጵያ ግን በፌዴራልም ሆነ በክልሎች ያለው ልምድ ገና መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ አማራ ክልል ቀደም ሲል ቦርዱ ከመቋቋሙ በፊት ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች በመነሳት ለባለሙያዎች ፈቃድ የመስጠት ስራ ሲያከናወን ነበር፡፡ ቦርዱ ከተቋቋመበት 2006 .ም ጀምሮ አሰራሩ ሊቀየር ችሏል፡፡ ነገር ግን «አዋጁ ሲወጣ የክልሎች ጉዳይ በአግባቡ አልታየም ነበር» የሚለት አቶ ስመኝ፤ በዚህም ምክንያት አንዳንድ ክልሎች የራሳቸው አዋጅ በሚፈቅደው መልኩ መስራትን እስከመምረጥ ደርሰው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

የክልላቸውን ተሞክሮ በተመለከተ፤ ዘርፉ በፌደራል ደረጃ ባለቤት አግኝቶ የሚሰራው እስከተገኘ ድረስ አሰራሩን ተቀብለው በክልሉ የሚገኙ የኦዲት ባለሙያዎችን ስም ዝርዝር አስረክበው ስራ ማቆማቸውን አቶ ስመኝ ያስታውሳሉ፡፡ ይሁንና ከ2008 .ም አጋማሽ ጀምሮ የቦርዱን ስልጣን በጠበቀ መልኩ በድጋሚ ክልሉ ፈቃድ የመስጠት ስራ ጀምሯል ይላሉ፡፡ አሁንም በዚሁ አሰራር መቀጠላቸውን በመጥቀስ፡፡ ይሄ ደግሞ እንደ አገር ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብና አዘገጃጀት ወጥነት እንዲጎድለው ያደርጋል፡፡

በአጠቃላይ በአዋጁ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ከተደረገው ውይይት መረዳት እንደሚቻለው ስራው አገራዊ እንደመሆኑ በፌዴራልና በክልሎች መካከል የተጠናከረ የአሰራር ቅንጅት ይፈልጋል፡፡ በተለይም በፌዴራል ደረጃ የወጣው አዋጅ አፈፃፀም የተማከለ መሆኑ ላይ የሕግ ጉዳይን በአግባቡ መፈተሽ ተገቢ ይሆናል፡፡ በውይይት መድረኩ መክፈቻ ላይ የተገኙት ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሐም ተከስተ ትኩረት ሰጥተው የተናገሩትም ይሄንኑ ነበር፡፡

ሚኒስትሩ እንደሚሉት፤ እስካሁን በነበረው ሂደት አዋጁ ላይ የሕጉን መንፈስና አላማ እስከመቀየር የሚደርስ ከፍተኛ ማሻሻያ ይደረጋል ተብሎ ባይጠበቅም፤ የባለሙያዎች ምዝገባና ቁጥጥር በተመለከተ ግን የተሻለ አማራጭ ወስዶ ለማሻሻል የሚያስችል ስራ ይከናወናል፡፡ በቅድሚያ ግን ዘርፉን ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ውስጥ በክልሎችና በፌደራል ደረጃ የተሻሉ የጋራ አማራጮችን ማመላከት አሁንም ሊታሰብበት የሚገባ ስራ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ውጤቱ የግብር ከፋዩን ሕዝብ ጥቅም የማስጠበቅ ጉዳይ ነውና፡፡

 

ብሩክ በርሄ

 

 

Published in ኢኮኖሚ

የሳኡዲ አረቢያ ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩ እንቅስቃሴ በማድረግ የምትታወቀው ማናል አል ሸሪፍ ፤

 

የሳኡዲ አረቢያ ሴቶች ለዘመናት መኪና የመንዳት መብት ተነፍገው መኖራቸው የአደባባይ እውነታ ነበር፡፡ የአገሪቱ ንጉስ ሳልማን በቅርቡ ይፋ ባደረጉት አዋጅ መንጃ ፈቃድ ለሚፈልጉ ሴቶች እንዲሰጣቸው ትእዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ መኪናም ማሽከርከር እንደሚፈቀድላቸው ተረጋግጧል። በሴቶች ላይ ተጥሎ የነበረው መንጃ ፈቃድ እንዳያወጡ መኪናም እንዳይነዱ የሚከለክለው እገዳ መነሳቱ በአጠቃላይ የሳኡዲ አረቢያን ሴቶች ከልብ አስደስቷል፡፡

በንጉስ የምትመራውና ወግ አጥባቂዋ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ሴቶች መንጃ ፈቃድ እንዳያወጡ መኪናም እንዳይነዱ ይከለክል የነበረውን ሕግ በመሻሩና በመፍቀዱ በሀገሪቱ ታሪክ ትልቅ ስርነቀል ለውጥ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ዜናውን ታላላቅ አለም አቀፍ ሚዲያዎች ቢቢሲ፤አሶሽየትድ ፕሬስ፤ሲኤንኤን እንዲሁም የአረቡ አለም መገናኛ ብዙሀን ሰፊ ሽፋን ሰጥተውታል፡፡ በፌስቡክና ትዊተርም ሰፊ አስተያየቶች ተስተናግደዋል፡፡

ጥብቅ በሆነው የእስላማዊ የሸሪአ ሕግ በምትመራውና በምትተዳደረው ሳኡዲ አረቢያ ለዘመናት ተከልክሎ የቆየው ሴቶች መንጃ ፈቃድ እንዳያወጡ መኪና እንዳይነዱ ይከለክል የነበረው ሕግ በመሻሩ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ቀድሞ ያልነበረና ያልታየ ስርነቀል ለውጥ ተደርጎ ተወስዶአል፡፡ በሀገሪቱ ለውጥ እንዲደረግ ሲጠይቁ ተቃውሞ ሲያሰሙ ለነበሩ አክቲቪስቶችም ትልቅ ድል ተደርጎ ተቆጥሯል፡፡

አንድ ሳኡዲ አረባዊት ሴት ስለጉዳዩ አንስታ ስትናገር «የአባቴን ወፎች ከጎጆአቸው ይውጡ የሚለውን ዘፈን አስታወሰኝ» ብላለች። አዋጁን ተከትሎ ሴቶች ከእንግዲህ የመንጃ ፈቃድ ለማግኘት ከአካባቢያቸው ጥበቃዎች ፈቃድ አይጠይቁም፡፡ ሲነዱም በመኪናቸው ውስጥ ጠባቂ አያስፈልጋቸውም ሲሉ አዲሱ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የተሾሙት የሳኡዲ አረቢያ አምባሳደር ልኡል ካሊድ ቢን ሳልማን ቢን አብዱል አዚዝ ተናግረዋል፡፡ እንደማስበው የእኛ አመራር ሕብረተሰቡ ዝግጁ መሆኑ ገብቶታል ሲሉ ለሪፖርተሮች ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተሮች ሳኡዲ አረቢያ የጠባቂዎችን ሕግ ለማቅለል አቅዳለች ወይ፤ ወይንስ የሴቶችን መብት ለማስፋት ሌሎች እርምጃዎችን ትወስዳለች በሚል ላቀረቡላቸው ጥያቄ ሳልማን አስተያየት አልሰጡም፡፡የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ለውጡን በማወደስ በትክክለኛው አቅጣጫ የተወሰደ ትልቅ እርምጃ ብሎታል፡፡

የንጉሱ ውሳኔ የመጣው በተያዘው ሰፊ የለውጥ ፕሮግራም መሰረት ሲሆን ባለፈው ሳምንት ሴቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በስፖርት ስታዲየም እንዲገቡ ተደርጓአል፡፡ ባሳኡዲ አረቢያ ግትርና ወግ አጥባቂ በሆነው ማሕበራዊ ስርአትና ጥብቅ በሆነ ሁኔታ የጾታ ሚና ላይ ገደብ በሚጥለው ሴቶች በሕዝቡ ውስጥ ያላቸውን ሚና በከባድ ሁኔታ ውስን በሚያደርግበት ሀገር አሁን የተገኘው ለውጥ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ እርምጃው በሳኡዲ ሕብረተሰብ ውስጥ በብዙ ጎኑ ለውጦችና ሽግግሮች በስፋት እንደሚያመጣ ይታመናል፡፡

አንድ የሳኡዲ መንግሥት ከፍተኛ ሚኒስትር የሳኡዲ ሕብረተሰብን ባሕላዊ አብዮት የኢኮኖሚ ለውጥን ተመስሎ ሲሉ ፈርጀውታል፡፡ በቅርብ ወራት በሪያድ ቀጥታ የኮንሰርት ስርጭት ታይቶቷል፡፡ ታዳሚዎቹ ወንዶች ብቻ ነበሩ፡፡ በአንድ ወቅት ግዙፍ አቅም የነበረው ኃይማኖታዊው ፖሊስ አቅሙ ቀንሷል፡፡

ሳኡዲ አረቢያ በአለማችን ላይ ሴቶች መኪና ከመንዳት የተከለከሉባት ብቸኛዋና የመጨረሻዋ ሀገር የነበረች ሲሆን ይህንን እውነት ተቺዎች የሀገሪቱ ሴቶች በአለም ላይ እጅግ በጣም የተጨቆኑ ለመሆናቸው ለማሳየት በማስረጃነት ይጠቀሙበታል፡፡ ሴቶች ባሳኡዲ አረቢያ መኪና መንዳት ሊፈቀድላቸው ይገባል የሚለው የቅርብ ዘመቻ የተጀመረው ከ10 አመት በፊት ሲሆን ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው በ2013 በሀገሪቱ መንገዶች ከመኪና ጀርባ የተቀመጡ በርካታ ሴቶች በፖሊስ በመታሰራቸው ምክንያት ነው፡፡

የሳኡዲ መንግስት ለሴቶች መንጃ ፈቃድ እንዲያወጡ መፍቀዱን ባስታወቀበት ወቅት መኪና በመንዳትዋ ታስራ የነበረችውና በዚህ ዘመቻዋ በሕዝቡ ዘንድ የምትታወቀው ማናል አል ሸሪፍ « አሁን በአለማችን የመጨረሻዋ የሆነችው ሀገር ሴቶች መኪና እንዲነዱ ፈቀደች፤ አሳካነውብላለች፡፡

ከዱባይ ወደ ሳኡዲ አረቢያ መኪና ለመንዳት ስትሞክር ተይዛ ከሁለት ወር በላይ በእስር ቤት ውስጥ ያሳለፈችው ሉጄይን ሀትሉል «ፈጣሪ ሊመሰገን ይገባል» ስትል በትዊተር ገጿ ጽፋለች፡፡ ጥብቅ የጥበቃ ሕግ የሚባለው ባሎች ወይንም አባቶች ሚስቶቻቸውን ወይንም ሴት ልጆቻቸውን የመንዳት ክልከላውን በሽፋንነት በመጠቀም ከቤት እንዳይወጡ ያደርጋሉ፡፡ ይህ በከፍተኛ ደረጃ ወግ አጥባቂ በሆነው ሀገር ውስጥ ለረጅም ጊዜ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ነበረው፡፡

በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የተመ ሰረተው ኮሚቴ ውሳኔው እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ለማጥናት 30 ቀናት አሉት፡፡ ዘ ጋርድያን ያነጋገራቸው የሳኡዲ ሴቶች ሕጉ በመለወጡ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ ተደርጓል ትላለች የ26 አመት እድሜ ያላት ሱልታና አልሳኡድ ከሪያድ፡፡ «ቤተሰቦቻችን እንዲቀበሉት አንጠብቅም፡፡ የምንጠብቀው ትልቅ ነገር እንደ ጀርባ አጥንት ሆኖ መንግስት እንዲረዳን ነው» ብላለች፡፡

ሱልታና አልሳኡዲ «ይህ ለሴቶች ግዙፍ እርምጃ ነው። ሴቶች መኪና ሲነዱ ማየት መልካም ነው። አሁን ሀገሪቱ በዝግታ ግን ደግሞ በእርግጠኝነት ወደእኩልነት መሬት እየተለወጠች ሲሆን፤ ይህ አስገራሚ ነው፡፡ እነዚህ የነጻነት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት እርምጃዎች ናቸው፡፡ ገና ወደ 2030 አልደረስንም» ስትል መንግስት የሳኡዲን ሕብረተሰብ ለመለወጥ እንዲሁም ለሴቶች ተጠቃሚነት ያወጣውን እቅድ አስመልክታ ተናግራለች፡፡ ሱልታና «የዚህ ትልቅ ራእይ አካል ነን፤እኛ ሴቶች አሁን ትኩረት አግኝተናል» ብላለች፡፡

በአዲሱ ሕግ መሰረት ሴቶች በሕጋዊ መንገድ የወንድ ጠባቂዎቻቸውን ሳያስፈቅዱ መንጃ ፈቃድ ማግኘት ይችላሉ፡፡ የጠባቂነት ሕግ ለሳኡዲ ወንዶች በሴት ቤተሰቦቻቸው ላይ ስልጣን ይሰጣቸዋል፡፡ የንጉሳዊው አዋጅ በተሰማ ከአንድ ቀን ባነሰ ጊዜ ውስጥ በመላ ሀገሪቱ ድንጋጤ እንደተፈጠረ የሳኡዲ ሴቶች ይናገራሉ፡፡ ማሕበራዊ ሕጎች በእስላማዊ አስተምህሮት የሚመሩ በመሆኑ፡፡

የአገሪቱ ከፍተኛ እስላማዊ ቀሳውስት ኮሚሽን « በሸሪአ ሕግ መሰረት የሕዝቡንና የሀገሩን ፍላጎት የተመለከተውን ንጉሥ ፈጣሪ ይባርከው» ሲል ትዊት አድርጎአል፡፡ የቀድሞው የኃይማኖታዊው ፖሊስ አዛዥ የነበሩት ዶክተር አብደል ላቲፍ አል ሼክ «የሴቶች መኪና መንዳት ጸረ ሸሪአ አይደለም፡፡ ሴቶች የበለጠ የሚስማማቸውን መምረጥ ይችላሉ» ሲሉ ትዊት አድርገዋል፡፡

በሳኡዲ አረቢያ የኃይማኖት ፕሮፌሰር የሆኑት ሼክ ካሊድ አል ሞስሌህ ሴቶች መኪና እንዲነዱ መፈቀዱ አብላጫ ቁጥር ያለውን ሕዝብ ጥያቄ መመለስ ነው፡፡ ለእርምጃው ትክክለኛነት በእስልምና ሕግ ረጅም ምክንያቶች አሉ ሲሉ ትዊት አድር ገዋል፡፡ አሁንም ብዙ የሚሰሙ ጭምጭም ታዎች አሉ፡፡የሸሪያ ሕግ ትልቅ ሚና ሊጫወት ይችላል፡፡ በአንዳንድ የሳኡዲ አካባቢ ከተወሰነ እድሜ በላይ ካልሆነ በስተቀር ሴቶች መንዳት አይችሉም የሰአት እላፊም ይኖራል የሚሉ ጭምጭምታዎች ይሰማሉ፡፡

የሳኡዲ አረቢያው አዲሱ ልኡል መሀመድ ቢን ሳልማን ሴቶች መኪና እንዲነዱ መፍቀድ የለውጡ ቁልፍ አድርገው ይመለከቱታል፡፡ እርምጃው በሠራተኛው ኃይል ውስጥ የሴቶችን ከፍተኛ ተሳትፎ ያሳድጋል፤ በሴቶችና በወንዶች መካከል ባለው ማሕበረሰባዊ ግንኙነት ውስጥ ያለውንም ውስንነት ከቤተሰብ ውጭ በአለውም ደረጃ ትልቅ ስርነቀል ለውጥ ያመጣል ነው የሚሉት፡፡

ልኡሉና አባታቸው ንጉሥ ሳልማን በለውጡ በፍጥነት መጓዝ ከመቶ አመታት በላይ ባስቆጠረውና ስር ሰዶ በኖረው በአብዛኛው ሀገሪቱ በተንሰራፋው አንዳንድ ግትር ትርጉም በሚሰጡት የሱኒ እስላማዊ አስተምህሮዎችን በሚከተሉና በቀሳውስቱ ተቋማት ቁጣ ሊያስከትል ይችላል የሚል ፍራቻ አላቸው፡፡

 

ወንድወሰን መኮንን

 

 

 

Published in ዓለም አቀፍ

 

እሬቻ በኦሮሞው ሕዝብ ዘንድ ለዘመናት ሲከበር የኖረና በመከበርም ላይ ያለ ታላቅ ሀገራዊ እሴት የሆነ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት በዓል ነው፡፡ በባሕሉ መሰረት እርጥብ ቄጠማ ይዘው ወንዝ ዳር በመውረድ በአባገዳዎች መሪነት ሕዝቡ ምርቃት የሚቀበልበት ድቅድቅ ከሆነው የክረምቱ ጨለማ አልፎ እነሆ የአመቱ መጀመሪያ ወደሆነው መስከረም ወር ደረስን ዘመኑን፣ ቤተሰቦቻችንን ሀገራችንን ሕዝቡን ደጁን ቀዬውን እርሻውን ሰብሉን አዝመራውን ከብቶቻችንን ባርክልን ብሎ ሕዝቡ በጋራ ተሰባስቦ በአባ ገዳዎች መሪነት ለፈጣሪ ምስጋና የሚያደርስበት ታላቅ በዓል ነው፡፡

በአሉ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት በአል እንጂ ፖለቲካዊ ተቃውሞ የሚሰማበት የሚስተናገድ በትም አይደለም፡፡ ሆኖም ተደርጎም አይታወቅም፡፡ አምና ተቃውሞ በሚያሰሙ ሰዎች በተቀሰቀሰው ሁከት በተፈጠረው መደናገጥና ትርምስ ሁሉም በየአቅጣጫው ለመውጣት በጀመረው ሩጫ ከህዝቡ ብዛት የተነሳ አንዱ በሌላው ላይ እየተራመደ ብዙ ዜጎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ አካላቸው ጎድሏል፡፡ በሰላም በአሉን ለማክበር ከቤታቸው ወጥተው ሳያስቡት በዚያው ድንገተኛ አደጋ ለቀሩት ወገኖቻችን የተሰማን ጥልቅ ሀዘን አልደበዘዘም፡፡ ይሁንና የዘንድሮው በአል በሰላም በመከበሩ ኃላፊነቱን አባገዳዎች ሕዝቡና መንግስት በጋራ ሆነው በመወጣታቸው በስነ ስርዓት በሆታ በምስጋና በምርቃት በጭፈራ በሰላም በመጠናቀቁ ደስታው የሁላችንም ነው፡፡

የአባገዳዎች ምክር ቤትም በአሉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም መጠናቀቁን አስታውቋል፡፡ ወትሮም የሰላሙ የሀገሩም ጠባቂና ባለቤት ሕዝብ ነውና የታየው ስነ ስርዓትና ጨዋነት የህዝቡን ታላቅነት የመሰከረ ደግሞ ደጋግሞ ያረጋገጠ ነው፡፡ ህዝብን አልፎ ሰላምን ለማደፍረስ የሚችል ምንም ነገር እንደማይኖርም የታየበት ነው፡፡ ምን ይፈጠር ይሆን ? ተብሎ የተሰጋውን ያህል በሰላም ተጀምሮ በሰላም መጠናቀቁ ሁሉንም ወገን የሚያኮራ ነው፡፡

የእሬቻ በአል የሰላምና የምስጋና በአል ነው። እንኳን ከጨለማው ክረምት ወደ ጸሀይዋ ደረስን፤ጮራዋ ፈነጠቀች በሚል በባሕሉ መሰረት ሕዝቡ በሀይቁ ወይንም በወንዙ ዳርቻ እርጥብ ቄጠማ ይዞ ከያለበት ተነስቶ ሄዶ በመውረድ በአባገዳዎች መሪነትና ምርቃት በጋራ ሁኖ ለፈጣሪ ታላቅ ምስጋና የሚያቀርብበት ነው፡፡

እሬቻ ወደ ውሃው እርጥብ ቄጠማ የሚወረወርበት ከብት ታርዶ የሚበላበት ባሕላዊ መጠጡም ቀርቦ ተመርቆ ሁሉም እየተመሰጋገነ ያለውን የሚካፈልበት ነው። ዘመኑን የሰላም የጤና የደስታ አድርግልን የሚለው በታላላቆች የሚሰጠው ምርቃት በተሰበሰበው ሕዝብ ተቀባይነት በአምባው ላይ የሚያስተጋባበት በበአሉ ተሳታፊዎች ልዩ የደስታ ስሜት በፊታቸው ላይ ጎልቶ የሚነበብበት፣ ዘመኑን መጪውን ወቅት በተስፋ ተሞልተው የሚቀበሉበት ልዩ በአል ነው፡፡

በአሉ በኦሮሞው ውስጥ በድምቀት ይከበር እንጂ በየአመቱ ወደስፋራው እየሄዱ የሚያከብሩት ከሁለም ብሔር ብሔረሰቦች የተወጣጡ ዜጎች ናቸው፡፡ በሂደት በአሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ባሕል ወደመሆን ተሸጋግሯል፡፡ እሬቻ በባሕልነቱ ጥንታዊና ዘመናትን ያስቆጠረው በትውልድ ፈረቃና ርክክቦሽ በዘለቀው አከባበሩ የእኛና የእኛ ብቻ የሆነ የማንነት መገለጫችን ነው፡፡

አባገዳዎች በመላው የኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ የተከበሩ አንቱ የተባሉ ምክራቸውና ዳኝነታቸው የሚሰማ በባሕላዊ ስርአቱ መሰረት የሕብረተሰቡ መሪዎችና አስተዳዳሪዎች ናቸው፡፡ የተጣላ የሚያስታርቁ በደል የፈጸመ የሰረቀ ሰው የገደለ በኦዳው (ዋርካው) ስር ሕዝብ በተሰበሰበበት ዳኝነት ተሰይመው ፍርድ የሚሰጡ በባሕሉ መሰረት አጥፊን የሚቀጡ ካሳ የሚያስከፍሉ በዚህም እርቅና ስምምንት የሚያወርዱ በሕብረተሰቡ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸው የተከበሩ የተወደዱም ናቸው፡፡

ከጥንት ጀምሮ በኖረው ባሕል ተበደልኩ የሚል ሰው ጣቢያና ፍርድቤት አይደለም የሚሄደው፡፡ አቤት ተበድያለሁ ብሎ የሚያመለክተወ አባገዳዎች ጋ ነው፡፡ የገዳው የጀማው ባሕላዊ ሹሞች እነርሱው ናቸውና፡፡ እነርሱ ከሚሰጡት ውሳኔና ፍርድ ውጭ ቃላቸውን አልፎ የሚሄድ የለም፡፡ በጥንታዊውና ዘመናትን ባስቆጠረው ባሕላዊው እምነት መሰረት የመረቁት ምሩቅ የረገሙትም እርጉም ይሆናል ተብሎ ስለሚታመን ሕዝቡ ከአያት ቅድመ አያቶቹ ሲወራረድ የመጣውን ባሕሉን ያከብራል፡፡ እንዲህ አይነት ድንቅ ባሕል ያላት ታላቅ ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡

አባገዳዎች በፈረቃ በተወሰነ አመት እየተፈራረቁ ይመራሉ፡፡ የኦሮሞ ባሕል ጥንትም ዴሞክራሲያዊ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው። ታላላቆች ይሰማሉ፤ ይከበራሉ፤ ይደመጣሉ፡፡

ገጣሚ፣ ደራሲና አንትሮፖሎጂስት የአለም ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን በስነፍጥረት በሰው ዘር መነሻነት፤በኦሮሞ ባሕል ሰፊነትና ምንነት፤ የሰው ዘር ግንድነት ላይ «እሳት ወይ አበባ» ከሚለው የግጥም መድበሉ ጀምሮ በበርካታ ረጃጅም ስለሰው ዘር ግንድና እንዴት ከኢትዮጵያ ተነስቶ እየተሻገረ የተለያየ ስም እየያዘ ባሕር ማዶውን አለምን እንደሞላው በሰላ ግጥሙ በአማርኛ በኦሮምኛ በግእዝ ጥልቅ እውቀቱ እየተነተነ ደግሞ ደጋግሞ አስነብቦናን፤ ነግሮናል፡፡ የገዳ ስርዓትና እሬቻንም «አባገዳ ... አባ ገልማ» በሚለው ጥልቅ ግጥሙ አወድሷል፡፡

የሰው ዘር በሙሉ በባሕሉ በእምነቱ በቋንቋው በመልክአምድር አሰፋፈርና አቀማመጡ ቢለያይም መነሻው ግን አንድ ግንድ መሆኑን በጎሳና በዘር ሊጋጭ እንደማይገባው መክሮ በተፈጥሮ ሕግ ተሸንፎ ያለፈለው የአለም ሎሬት ጸጋዬ በዚያ አቻምየለህ ብዕሩ አባገዳዎችንና የገዳ ስርአቱን ጥንታዊነት የባሕሉን ግዝፈት የስነ ስርዓቱን ታላቅነት ዘመን በማይገድፈው መልኩ ሕያው አድርጎ ጽፎት አልፎፏል፡፡

ኢልማ ገልማ

አባ ገዳ ርቱእ ጀማ

ብፁእ ጀማ

ለካ አንተ ነህ

አባ ገዳ ኢልማ ገልማ

ያደ ኦሮሞ ሻማ

ዋቃ ገዲ ነማ ኦሊን ሱማ

አከ ሱማ

የተሰኘዉ እንደ አክሱም

የተባልከዉ ፍፁም ጀማ

ለካ አንተ ነህ

አገ ኦጋ

ጂገ ሎጋ

አባ ሰርዳ

አባ ገዳ

አባ ፈርደ ነበልባሉ

እም ቅድመ ኦሪት ባህሉ

ያኢ ቢያ አባ ቃሉ

የማይቀለበስ ቃሉ

ለካ አንተ ነህ

እያለ ከዘመን ዘመን ተሸጋጋሪ በሆነ መልኩ በሀውልትነት ተክሎት አልፎአል፡፡ታላቁ ሰው ሎሬት ጸጋዬ፡፡ እንደ ኦዳ እንደ ዋርካው ጸጋዬም ሀገሩን ባሕሉን ያነገሰ ታላቅና ግዙፍ ዋርካ ነበረ፡፡

የእሬቻ በአል ከኦሪት ጊዜ ጀምሮ ሲከበር የኖረ እጅግ ጥንታዊ የምስጋና ባሕል ነው፡፡የፍቅር የመከባበር የሰላም የአብሮነት በሕብረት በአንድነት ያለልዩነት ለዚህ ቀን ያደረስከን አምላክ የቀጣዩም ዘመን ሰው በለን አትለየን፤ የዘራነው ይባረክ ገበያውን ጥጋብ ሀገሩን ሰላም አድርግልን ብለው በአባገዳዎች መሪነትና ምርቃት በሕዝቡ ተቀባይነት በዜማ በጭፈራ በሆታ በደስታ በባሕላዊ አለባበስ የሚከበር ታላቅ በአል ነው፡፡

የእሬቻ በአል ጥንታዊነት ግን ለክርክር አይቀርብም፡፡ የእምነት፣ የባሕልና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በሕገመንግስቱ የጸደቀና ሕጋዊ ዋስትና ያለው ነው፡፡ ሁሉም የእኔ የሚለውን በነጻነት በሰላም የሌሎችን መብት ሳይነካ አንዱ የሌላውን እንደራሱ አክብሮ ማክበር ይችላል፡፡ ነጻነት ይሄ ነው፡፡ እሬቻ የሰላም የፍቅር ተቻችሎ የመኖር የመከባበር በጋራም ፈጣሪን የማመስገን ጥንታዊ የሆነ ለዘመናት ሲከበር የኖረ ልዩ ባሕላችን ነው፤ እንጠብቀው ለትውልድ እናስተላልፈው።

 

መሐመድ አማን

 

 

Published in አጀንዳ

 

ወቅቱ በመላው አገሪቱ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት ትምህርት የሚጀምሩበት ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩት ተማሪዎች በየደረጃቸው ወደተዘጋጀላቸው የእውቀት ገበታ ስፍራ ሲያቀኑ፤ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ደግሞ ከአገር ውጭ በሚያገኙት የትምህርት እድል ለመጠቀም ባህር ይሻገራሉ። ያገኙትን እውቀት ይዘው የሚመለሱ እንዳሉ ሁሉ፤ በዛው የሚቀሩም በርካታ ናቸው። በተለያየ ደረጃ የሰለጠኑ የታዳጊ አገራት ዜጎች የተሻለ የኑሮ ደረጃ፣ከፍተኛ ክፍያ፣ የረቀቀ ቴክኖሎጂና የረተጋጋ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ያለባቸውን አገራት በመምረጥ ባገኙት የትምህርት እድል ተጠቅመው ወደ ውጭ ወጥተው ሲቀሩ ይስተዋላል።

አብዛኛው የአፍሪካ አገራት ታዳጊ በመሆናቸው በከፍተኛ ደረጃ ለተማረ የሰው ሀይል ፍልሰት የተጋለጡ ናቸው። ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) እ አ አ በ2012 ይፋ ባደረገው ጥናት እ አ አ ከ1990 ጀምሮ በየአመቱ 20 ሺ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ አፍሪካውያን ወደ አደጉት አገራት ሄደው ይቀራሉ። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ምክትል ዋና ጸሀፊ የነበሩት ዶክተር ላላ ቤን ባራክ በአንድ ወቅት የስጋቱን ከፍተኛ መሆን አስመልክቶ «መንግስታት የተማረ የሰው ሀይላቸውን በአገራቸው ለማስቀረት ከፍተኛ ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል፤ ይህን ካላደረጉ ከ25 አመታት በኋላ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ የልሂቃን እጥረት ይገጥማቸዋል» ብለዋል።

የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታም በተመለከተ የአህጉሪቱ እጣ ፈንታ ተጋሪ ስለመሆኗ ጥናቶችን ዋቢ አድርጎ መጥቀስ ይቻላል። የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ጥናት እንደሚያመለክተው፤ ካለፉት አስር እስከ አስራ አምስት አመታት ባለው ጊዜ ወደ ውጭ ከሄዱት ኢትዮጰያውያን ሃምሳ በመቶው ወደ አገራቸው አልተመለሱም። በአሜሪካ ቺካጎ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ሀኪሞችም በአገራቸው ከሚገኙት በቁጥር ይበልጣሉ።

የተማረ የሰው ሀይል ወደ ውጭ የሚፈልስባቸውን ምክንያቶች በሁለት ከፍሎ መመልከት ይቻላል። የመጀመሪያው ባለሙያዎችን ከአገር እንዲወጡ የሚገፏቸው (Push Factors) የሚባሉት ሲሆኑ ከውጭ ደግሞ የሚስቧቸው (Pull Factors) ይባላሉ። ባለሙያዎችን ከውጭ የሚስቧቸውን ጉዳዮች ማስቀረት ባይቻልም ወደ ውጭ የሚገፏቸውን ምክንያቶች በመፈተሽ ማሻሻል ይቻላል፤ ይገባልም።

በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ወደ ውጭ ከሚገፏቸው ምክንያቶች መካከል ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ ተጠቃሽ ነው። የሰለጠኑ ባለሙያዎች በዚህ የተነሳ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ሲቸገሩ ይታያሉ። ይህ የባለሙያዎችን ፍልሰት እንዳያባብስ መንግስት የተለያዩ አማራጮችን ለመተግበር እየሞከረ እንደሚገኝ ይታወቃል። ለአብነትም ሀኪሞች ከመደበኛ የስራ ሰአታቸው ውጭ በማገልገል ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ዳኞችና መምህራን በአነስተኛ ዋጋ ቤት እንዲያገኙ የሚሰራው ስራ ተጠቃሽ ነው። ይህ ጅምር መልካም ቢሆንም በሁሉም የሙያ መስክ ማስፋት፤ እንዲሁም የተጠቃሚነት ደረጃውን ከሌሎች አጋራት ጋር በማነጻጸር ማሻሻል ይጠበቃል።

ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠር ብዙ ዋጋ የሚያስወጣ ጉዳይ አይደለም። በርካታ ባለሙያዎችን ከአገር የሚያሸሽ አንድ ምክንያት ሆኖ ስለሚነሳ በከፍተኛ ወጪ አገር ይጠቅማሉ ተብለው ለሰለጠኑ ባለሙያዎች የተመቻቸ የስራ አካባቢን መፍጠር ሊታሰብበት ይገባል።

በርካታ ባለሙያዎች በአገራቸው በተለያየ የቴክኖሎጂ መስክ ስልጠና ቢያገኙም ያን የሚመጥን የስራ እድል ባለማግኘታቸው ወደ ውጭ ወጥቶ መስራትን እንደ አማራጭ ይወስዱታል። ይህን ከመሰረቱ ለመቀየር የሰለጠኑት ባለሙያዎች በአገሪቱ እየተስፋፉ ከመጡት የኢንዱስትሪ ዞኖችና ዘመናዊ ፋብሪካዎች ጋር የማስተሳሰር ጉዳይ ወቅቱ የፈጠረው እድል በመሆኑ ትኩረት ይሰጠው።

ዜጎች ወደ ውጭ እንዲያማትሩ የሚያደርጉት የአካዳሚክ ነጻነት አለመከበር፣ የተረጋጋ ማህበራዊና የፖለቲካ ሁኔታ አለመኖር እንዲሁም ሌሎች መሰረታዊ እክሎች ተፈትሸው ከህዝብ በተሰበሰበ ሀብት እየሰለጠኑ ለባእድ አገር መጠቀሚያ የሚሆኑብት አካሄድ ሊገታ ይገባል። ሂደቱ የሰለጠነ የሰው ሀይልን በቁጥርና በጥራት በመቀነስ በልማት ወደ ፊት ለመገስገስ የሚደረገውን ጥረት ያቀዘቅዛል፣ የፈጠራ ተሰጥኦ ያላቸውን ዜጎች ያሳጣል፣ ለተለያዩ ቴክኒካል እገዛዎች ለውጭ ባለሙያዎች ጥገኝነት ይዳርጋል። በተጨማሪም ዘገምተኛ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር በር ስለሚከፍት በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል።

ምንም እንኳን ዜጎች ወደ ውጭ በመውጣት ከሚልኩት ገንዘብ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ የአገር ኢኮኖሚን በመደገፍ አስተዋጽኦ ያበረክታል የሚል መከራከሪያ ቢነሳም በአገር ውስጥ ቀርተው ለለውጥ እና ለእድገት የሚጫወቱት ሚና ስለሚጎላ የተማረ የሰው ሀይል ፍልሰት እንዲገታ ሁሉም ባለድርሻ አካል የሚጠበቅበትን ይወጣ። በተለያየ ምክንያት በውጭ የሚገኙ የሰለጠኑ ባለሙያዎችም አገራቸው የዋለችላቸውን ውለታ በማስታወስ ብድራቸውን ለመክፈል ሊተጉ ይገባል !

 

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ

 

ታዳጊ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን እንዲቋቋሙ የሚደረገው ድጋፍ የህብረተሰቡን ህይወት የሚቀይሩ ዘርፎች ላይ እንዲያተኩር ኢትዮጵያ ግፊት የምታደርግ መሆኗን የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ግሎባል ኢንቫይሮሜንታል ፋሲሊቲ (ጂ ኢ ኤፍ) የተሰኘ ዓለም አቀፍ ተቋም የበለጸጉ አገራት ለታዳጊ አገራት የሚያደርጉት ድጋፍ በመጠን እና በጥራት እንዲጨምር ለማድረግ ለሁለት ቀናት የሚቆይ የምክክር መድረክ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ እያካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቃሬ ጫዊቻ እንደተናገሩት፤ ታዳጊ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ የበለጸጉት አገራት የገንዘብ ድጋፍ በህብረተሰቡ ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ በሚያመጣ አኳኋን መሆን እንዳለበት ኢትዮጵያ አቋሟን ታራምዳለች፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመቋቋም እና ለመመከት የሚከናወነው ጥረት የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያስገኝ የበለጸጉት አገራት ድጋፍ በመጠን እና በጥራት እንዲጨምር ከማድረግ ባሻገር ገንዘቡ በሂደት እንዳይባክን ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡

የበለጸጉ አገራት በተለያዩ መንገዶች ታዳጊ አገራትን ለመደገፍ ቃል ገብተው ብቻ የሚያልፉት ሳይሆን ድጋፉ ዋስትና ያለው መሆን እንዳለበትም ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ቃሬ ጠይቀዋል፡፡ ጂ ኢ ኤፍ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና ለአካባቢ ጥበቃ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ያነሱት አቶ ቃሬ በተለይም የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማልማት፣ ለብዝሃ ህይወት ጥበቃ፣ ጎጂ ኬሚካሎችን ለማስወገድ የሚያስችል የቴክኖሎጂ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል እና የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን፤ እገዛው የሚፈለገውን ያህል እንዳልሆነ አንስተዋል፡፡

የግሎባል ኢንቫይሮሜንታል ፋሲሊቲ (የጂ ኤ ኤፍ) ሥራ አስኪያጅ ዋና አማካሪ ክላውስ አስትራፕ በበኩላቸው፤ ተቋሙ ለአካባቢ ጥበቃ ፈንድ የሚያሰባስብ ሲሆን አየር ንብረት ለውጥ፣ የመሬት መንሸራተት፣ ኬሚካሎችን ለማስወገድ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ40 ታዳጊ ሀገራት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡ የሚደረገው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ እና የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም የአካባቢ ጉዳዮች አሳሳቢነት እያደጉ በመምጣታቸው የምክክር እና የውይይት መድረክ ማካሄድ ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡

ሚስተር ክላውስ ይህ ምክክር በቀጣይ ወራትም በብራዚል እና በስዊድን እንደሚካሄድ የገለጹ ሲሆን፤ የበለጸጉት አገራት የሚያደርጉትን ድጋፍ መጠን ከፍ ለማድረግ ከስምምነት ለመድረስ ያስችላል የሚል እምነት እንዳላቸው አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማትን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ጎን ለጎን ለማስኬድ ጥረት ከሚያደርጉ አገራት መካከል ተጠቃሽ መሆንዋን ያነሱት ሚስተር ክላውስ የምክክር መድረኩ በኢትዮጵያ መካሄዱ ተቋሙ ያነገበውን ዓላማ ለማሳካት እገዛ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

 

መላኩ ኤሮሴ

Published in የሀገር ውስጥ

ከአውደጥናቱ ተሳታፊዎች በከፊል

 

.. አ በ2030 ለማሳካት የታቀዱት 17 የዘላቂ ልማት እቅዶች ከኢትዮጵያ የልማት እቅዶች ጋር በማጣመር መስራት እንደሚገባ የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ገለፀ።

በሚኒስቴሩ ትናንት በኔክሰስ ሆቴል የተካሄደው አውደ ጥናት የተዘጋጀው የዘላቂ የልማት ግቦችን በአሁኑ ወቅት እየተተገበረ ካለውና ከቀጣዮቹ ሦስተኛና አራተኛ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶች ጋር በማጣመር እንዴት መስራት እንደሚቻል ለመወያየት ታስቦ ነው።

ዓውደ ጥናቱ በተካሄደበት ወቅት የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንደተናገሩት፤ በውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ዘርፍ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የተያዙት እቅዶችን ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር ለማጣመር ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ዓውደ ጥናቶች የልማት ግቦቹን በየዘርፉ በመከፋፈል ለመተግበር ያስችላሉ። ዝርዝር ሥራዎችንም በመመልከት ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ምን እንደተከናወነና በቀጣይ እንዴት ማሻሻል እንደሚቻል መፍትሄ የሚጠቁሙም ናቸው፡

ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ፣ ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦችን ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ጋር በማጣጣም ለመስራት የገንዘብ አቅም እየፈተናት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እያንዳንዱ ሥራ በአግባቡ ቢታቀድም የታሰበውን ያህል ለማከናወን የገንዘብ እጥረት መኖሩን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ የገንዘብ ችግሩን ለመፍታት አጋር የልማት ድርጅቶች የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ጽሑፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህር ፕሮፌሰር ሰሙ አያሌው እንደተናገሩት፤ ሁሉም አገራት የዘላቂ ልማት ግቦችን ከአገራቸው ዕቅድ ጋር በጋራ በማስተሳሰር እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ አገራት መካከል ኢትዮጵያም አንዷ ስትሆን፣ ግቦቹን ለማሳካት እያንዳንዱን የልማት ግቦች ለሁሉም ባለድርሻ አካላት በመከፋፈል በትኩረት እንዲሰሩበት ማድረግ ይገባል፡፡

ፕሮፌሰሩ እንዳሉት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የታቀደው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እስካሁን ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር በማጣጣም የተሰሩት ሥራዎች 60 በመቶ ያህል መድረስ ችሏል፡፡ ይህን ማከናወን በመቻሉም ኢትዮጵያ በ2030 የተቀመጡትን የዘላቂ ልማት ግቦች የማሳካት ዕድሏ ሰፊ ነው፡፡

በአጠቃላይ የ2030 ግቦችን ለማሳካት በገንዘብ፣ በቁርጠኝነት፣ በሰው ኃይል፣ በአቅም ግንባታ፣ በትንበያ እንዲሁም ሌሎችንም ክፍተቶች ለመሙላት ትልቅ ጥረት የሚጠይቅ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ከመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጉድለቶች መማር እንደሚገባ ተናግረው፤ እስካሁን ከተሳኩት ይልቅ ቀሪ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ዓውደ ጥናቱ ዛሬ የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ በቀጣይ በሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እንደሚካሄድ ታውቋል።

 

ሰላማዊት ንጉሴ

 

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።