Items filtered by date: Friday, 06 October 2017

አቶ ነጻነት ታከለ

 

በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) ውድድር የፊታችን እሁድ እንደሚጀመር ፌዴሬሽኑ አስታወቀ፡፡ ውድድሩ ከ1998 .ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፤ ለ12ኛ ጊዜ በሚካሄደው ውድድር አዳማ ከነማና ጅማ አባጅፋር በተጋባዥነት እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡

የከተማዋ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነጻነት ታከለ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንዳሉት በየዓመቱ አዲሱ የውድድር ዘመን (የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ) ከመጀመሩ በፊት እንደ ቅድመ ውድድርና የአቋም መለኪያ ዝግጅት የሚያገለግለው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) እሁድ መስከረም 28 ቀን 2010.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም በደማቅ ሁኔታ ይጀመራል።

ውድድሩ ላለፉት 11 ዓመታት በከፍተኛ ፉክክር መካሄዱንና ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 12 በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚካሄደው 12ኛው ውድድር ስድስት የከተማው ክለቦች እንዲሁም ሁለት ተጋባዥ ክለቦች ተሳታፊ እንደሚሆኑ አስታውሰው፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ደደቢት ፣ መከላከያ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ አዲስ አበባ ከነማ ፣ አዳማ ከነማና ጅማ አባጅፋር የዘንድሮው ሻምፒዮና ተሳታፊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ነጻነት ገለጻ፤ በምድብ ድልድል የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓቱ መሰረትም በሁለት ምድብ ተከፍሎ በሚካሄደው ውድድር በምድብ አንድ የተደለደሉት ኢትዮጵያ ቡና፣ ደደቢት፣ አዲስ አበባ ከተማና ጅማ አባ ቡና የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን የፊታችን እሁድ መስከረም 28ቀን 2010 .ም የሚያደርጉ ሲሆን፣ በምድብ ሁለት ላይ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አዳማ ከተማ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክና መከላከያ ደግሞ ማክሰኞ መስከረም 30 ቀን 2010 .ም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ለ11 ዓመታት ሲካሄድ የቆየውን የመዲናዪቱ ከተማ የክለቦች ውድድርን ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአራት ጊዜያት ያህል በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና እና አምና ቅዱስ ጊዮርጊስን 10 መርታት የቻለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሦስት ሦስት ጊዜ በማሸነፍ ተከታዩን ደረጃ ሲይዙ በዘንድሮው ዓመት የፈረሰው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ ጊዜ ማሸነፍ ችሏል።_

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ አቶ ነጻነት ታከለ የሲቲ ካፕ ውድድሩን ሁለንተናዊ አንድምታ አስመልክቶ በርከት ያሉ ሀሳቦችን የሰነዘሩ ሲሆን፤ ቀጥሎ በተነሱት ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት ከጋዜጣው ሪፖርተር ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ በተለይም የእስካሁኑን የውድድር ተሞክሮ እና የዘንድሮው ከአሁን በፊት ከነበሩት መርሐ ግብሮች ምን እንደሚለየው እንዲሁም ስለተሳታፊ ክለቦች የአመራረጥ ሂደትና መሰል ጉዳዮች ላይ እንደሚከተለው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

11ዓመት ተሞክሮ

11 ዓመት ያክል ሲደረግ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) ለስፖርት ደጋፊው፣ ለስፖርተኛውና ለክለቦች መጠናከር ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮ ያለፈ ሲሆን፤ ተሳታፊዎች እርስ በርስ ልምዶችን እንዲለዋወጡ አስችሏል፡፡ የዘንድሮውም 12ኛው የሲቲ ካፕ ውድድር ሲዘጋጅ ትልቅ ስፖርታዊ ትርጉም እንደሚሰጥና በዓይነቱም ለየት ያለ የውድድር መድረክ እንደሚሆን ታምኖ ሲሆን፤ ከምንም በላይ የፌዴሬሽኑን የፋይናንስ አቅም ከመደገፍ አንጻርና ሌሎች ውድድሮች ሳይስተጓጎሉ እንዲቀጥሉ ለማድረግ አዎንታዊ ሚናን ይጫወታል፡፡ ባለፉት ዓመታት በተደረጉ ውድድሮች የተሳተፉ ክለቦችም መልካም ተሞክሮን በመቀመር ለዋናው ፕሪሚየር ሊግ የቅድመ ዝግጅት ተሳትፎን እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል በማለት አቶ ነጻነት አብራርተዋል፡፡

የዘንድሮውን ውድድር ልዩ የሚያደርገው

የዘንድሮ ዓመት ውድድሩን ለየት ለማድረግ ከተሰሩ ሥራዎች አንዱ የሽልማት አሰጣጥ ሥርዓት ነው፡፡ ይኸውም ከዚህ በፊት የዋንጫ ሽልማት ሲሰጥ የነበረው ለአዲስ አበባ ክለቦች ብቻ የነበረ ሲሆን፤ ከሌሎች ክልሎች የመጡ ተሳታፊዎች አሸናፊ እንኳን ቢሆኑ የልዩ ዋንጫ ተሸላሚ እንጂ መደበኛውን የዋንጫ ሽልማት አያገኙም ነበር፡፡ ሆኖም በአሁኑ ውድድር ደንቡን በማሻሻልና የስፖርቱ ቤተሰብ እንዲወያይበት በማድረግ የአሸናፊነትና የጠንካራ ውድድር መንፈስ እንዲኖረው በሚል የብዙ ባለ ድርሻ አካላት አስተያየት በውድድሩ ላይ አሸናፊ የሆነው ማንኛውም ክለብ በሚያገኘው ውጤት መሰረት የዋንጫው ተሸላሚ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ የክልል ተጋባዥ ክለብም ቢሆን ቢያሸንፍ ለውድድሩ የተዘጋጀውን የዋንጫ ሽልማት ይወስዳል ማለት ነው፡፡ ይህም የከተማ ዋንጫውን የፉክክር መንፈስ እንደሚያበረታታ በጽኑ መታመኑ ከወትሮው የውድድር መድረኮች የተለየ ያደርገዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከውድድሩ ከሚገኘው ገቢ ለጊዜው የማይጠቀስ ሽልማት በልዩ መልኩ ለማዘጋጀት ታስቧል፡፡ ይህም ለውድድሩ የተለየ ድባብ ይፈጥራል የሚል እምነት እንዳላቸውም አቶ ነጻነት አብራርተዋል፡፡

ሌላው የውድድሩ ድምቀትና የተለየ ገጽታ እንዲኖረው የሚያደርገው ነገር ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ባለፈው ዓመት ተሳትፎ ያላደረገው የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ስፖርት ቡድን በዘንድሮ ዓመት ለመሳተፍ ፍቃደኛ ሆኖ በመገኘቱ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ተወዳጅነትን የሚያተርፍ የውድድር መድረክ እንደሚሆን በተስፋ ተቀምጧል፡፡

የመረጃ ሥርጭቱም ቢሆን ከአሁን ቀደም በነበረው ለዘብተኛ አካሄድ ሳይሆን ማህበራዊ ሚዲያዎችን ጭምር በመጠቀም ሁሉንም ሚዲያዎች በአግባቡ በመጠቀም የዘመነ የመረጃ ልውውጥ ይደረጋል፡፡ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ችግሮችን ከመላቀቅ ጋር ተያይዞ፤ ችግሩን ሙሉ በሙሉ አብርደን ባልጨረስንበት ሁኔታ በትግል ሥራውን ጎን ለጎን መስራታችን የሥራ አስፈጻሚውን ጥንካሬ የሚያሳይ ተግባር እየተከናወነ መሆኑ በበጎ መልኩ የሚጻፍ ታሪክ ነው፡፡ ይህም ከባለፉት ጊዜያት የተሻለ የመነሳሳት መንፈስ ተላብሰው የሚሰሩ አስፈጻሚዎች መኖራቸውን የሚያመላክት ከመሆኑም ባሻገር ውድድሩ በጥሩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንዲቋጭ የየበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያበረክት ልዩ ሥራ መሆኑንም አቶ ነጻነት አክለው አስረድተዋል፡፡

የተሳታፊ ክለቦች ምልመላ መስፈርቶች

በመዲናዋ በፕሪሚየር ሊጉም ይሁን በተለያዩ ዲቪዚዮኖች ተካተው የሚሳተፉ በርካታ ክለቦች ቢኖሩም እነዚህን ሁሉ ማሳተፍ ስለማይቻል በዚህ የከተማ ዋንጫ ውድድር ላይ ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች ብዙ መመዘኛዎች ቀርበውባቸው እንዲሳተፉ የተደረገ ሲሆን፤ የምልመላ መስፈርቱ በቀዳሚነት በፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ የሆኑትን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ክለቦቹ ባላቸው ደጋፊና ተቀባይነት እንዲሁም ለፌዴሬሽኑ ሊያስገኙ ከሚችሉት ገቢ አንጻር ታሳቢ የተደረገ ሲሆን፤ በውሳኔዎቹ የትኞቹ ቡድኖች ይሻላሉ የሚለውን ፌዴሬሽኑ ተወያይቶ ያጸደቅነው ጉዳይ ነው፡፡ በተጋባዥነት የተመረጡ ሁለቱ ቡድኖች (አዳማ ከነማና ጅማ አባጅፋር) እንደ አዲስ አበባ ክለቦች በተመሳሳይ መስፈርት ነው፡፡

ከነገ በስቲያ በሚጀመረው ውድድር ላይ ከሚሳተፉት ክለቦች ውስጥ ስድስቱ የከተማዋ ክለቦች ሲሆኑ ከእነዚህም ውስጥ በ2010.ም የውድድር ዘመን በፕሪሚየር ሊጉ የማናየው የአዲስ አበባ ከተማ ቡድን አንዱ ይሳተፋል፡፡ ቡድኑ የተመረጠበት አግባብነት የከተማዋን ስም በመያዙ፣ በከንቲባው የሚመራ የህዝቡ ክለብ እንደመሆኑና የደጋፊና የህብረተሰቡ ጥያቄ እየበዛ በመምጣቱ እንዲሁም አስቀድሞ ጥያቄ በማቅረቡ ነው፡፡

የእጣ አወጣጥ ሥርዓት

የክለቦቹ ድልድልና የእጣ አወጣጥ ሥርዓቱ ባሳለፍነው ማክሰኞ በኢትዮጵያ ሆቴል የተደረገ ሲሆን፤ የውድድር መተዳደሪያ ድንብንና ህግ በጠበቀ መልኩ ሁሉም ተሳታፊ ክለቦች ተወካዮቻቸውን እንዲልኩ ተደርጎ ግልጽነት በተሞላበትና ሊያስማማ በሚችል እንዲሁም ጥያቄ ባልተነሳበት ሁኔታ በጋራ ማከናወን ተችሏል፡፡ የግልጽነቱ ዳርቻም በሚዲያዎች እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡

ከውድድሩ የሚገኙ ጠቀሜታዎች

ውድድሩ በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን፤ ፌዴሬሽኑ ከመንግሥትና ከማንኛውም አካል እገዛ ነጻ በመሆን ራሱን ችሎ በሚያገኘው በጀት የሚንቀሳቀስ እንደመሆኑ በፌዴሬሽኑ ስር የሚደረጉ የተለያዩ ውድድሮች የሚካሄዱት ከሲቲ ካፕ ከሚገኘው ገቢ ነው፡፡ ይህም ተተኪ ስፖርተኞችን በማብቃት ረገድ የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡ ከውድድሩ የሚገኘው ገቢ ከዚህም አልፎ ለሚወጡ ወጪዎችና ለሠራተኞች የሚከፈል በመሆኑ ትልቅ አቅም መፍጠሪያ የውድድር መድረክ ነው ማለት ይቻላል፡፡

በሌላ መልኩ ተጫዋቾች ራሳቸውን የሚፈትሹበትና አቋማቸውን የሚለኩበት በመሆኑ ብርቱ ተፎካካሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡ አጋጣሚው አንዱ ከአንዱ ልምድ የሚቀስምበትና የት ቦታ ላይ እንዳሉ የሚያውቁበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ ከዚህ ባለፈ ክለቦች መልካሙን አጋጣሚ ተጠቅመው አቋማቸውንና ያሉበትን ደረጃ እንዲፈትሹ ይረዳቸው፡፡ የውድድር መድረኩ የከተማ ዋንጫ እንደመሆኑ መጠን ደጋፊዎችም በጉጉት የሚጠብቁትና ለክለቦቻቸው ድጋፍ እንዲሰጡ በር የሚከፍት በመሆኑ ጥቅሙ ደጋፊንም ያካተተ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህም ደጋፊንና ስፖርተኞችን በማስተሳሰር የስፖርት እምርታው ከፍ እንዲል ያደርጋል፡፡

የፌዴሬሽኑና ሥራ አስፈጻሚ አካላት ድጋፍ

በፌዴሬሽኑ የሚደረጉ ድጋፎችን አስመል ክቶ፤ ፌዴሬሽኑ ከሚዲያ አካትና ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር በመሆን የሚሰራ ሲሆን፤ በተለይ የውድድር ቦታዎችን የማመቻቸት፣ የሚመለከታቸውን አካላት በመጋበዝ ውድድሩ ሰላማዊነቱን ተላብሶ እንዲካሄድ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር የመስራት፣ ደንብ በመቅረጽና ደንቡን ተግባራዊ የማድረግ፣ ለውድድሩ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የማሟላትና ስፖርቱን በሰፊው ተደራሽነት እንዲኖረው የማደረግ ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ ውድድሩን የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበላይነት እንደመምራቱ መጠን በእያንዳንዷ እንቅስቃሴ የሰው ኃይል መድቦ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ እኛም ዕድሉን ፈጥረን ተወዳዳሪዎችን ወደዚህ ማምጣታችን የፌዴሬሽኑን ትልቅ ተግባር የሚያመላክት ነው፡፡ በሥራ አስፈጻሚው አካላት በኩልም የውድድሩን ሂደትና ክዋኔ የሚመለከቱ ድጋፎች የሚደረጉ ይሆናል፡፡

የስታዲየም መግቢያ ዋጋ

ሙሉ ውድድሩ ከመስከረም 28 ቀን 2010 .ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት 12 ቀን 2010 .ም በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚደረግ ሲሆን፤ የስፖርት ቤተሰቡና የየክለቦቹ ደጋፊዎች በክፍያ በስታዲየሙ ገብተው ጨዋታዎችን መከታተል የሚችሉ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት የመግቢያ ዋጋው ክቡር ትሪቡን 150 ብር፣ ጥላ ፎቅ 100 ብር፣ ከማን አንሼ በወንበር 50 ብር፣ ከማን አንሼ ያለ ወንበር 20 ብር፣ ካታንጋ 20 ብር፣ ዳፍትራክና ሚስማር ተራ 10 ብር እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የስፖርት ቤተሰቡና ደጋፊውን የውድድሩን ቋሚ መርሀ ግብር አውቆ ድጋፉን መስጠት ይችላል፡፡ በመርሐ ግብሩ ሴቶችን ለማሳተፍ እቅድ የነበረን ቢሆንም፤ ከጊዜና የፌዴሬሽኑ ችግር አኳያ ይህ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በቀጣይ የውድድሩ መድረኮች የሚስተካከሉበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡

 

አዲሱ ገረመው

 

 

Published in ስፖርት
Friday, 06 October 2017 18:45

ከሰ ይጣን ወጎች

 

ሰይጣን ዓለምን በጠና አፈቀረ ኢትዮጵያንም የፍቅር መቀስ አላት

ሰይጣን ሰይጡ ሰይጣንቲ ሰይጣናለም በጠና ፍቅር ተይዞ ፍቅር… ፍቅርቅር… ፍቅርቅርቅር አደረገላችሁ፡፡ ከወደ ሲኦል አፈንግጦ የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው የፍቅር ግለቱ በርትቶ ዓለምን በእጁ ለማስገባት እያኮበኮበ ነው፡፡

ወሬው በተባራሪ አጨናባሪ እርኩስ መንፈስ አማካኝነት ከእጄ ላይ ወደቀ፡፡ መቼም ሰይጣንና ሰራዊቱ ውሸታም ቦጠሊቃ ትርትር የሆነውንም ያልሆነውንም የሚያወራ አሳባቂ መሆኑን እያወቅክ እንዴት ተቀበልክ ልትሉኝ ትችላላችሁ፤ ያላችሁኝን ብትሉ እኔ ግን የተባልኩትን አምኛለሁ እንዴት ካላችሁ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡

አጅሬው ጨለምተኛ ጨለማን ለብሶ ጨለማን ተጎናጽፎ ጨለማ ዙፋን ላይ እንደተቀመጠ ቁልቁል ምድሪቱን ዓለምን ተመለከተ፡፡ ዓለም የቴክኖሎጂዋን ያህል በኃጢአት ፖሊሲ ተጨማልቃ፤ በመጥፎ የፖለቲካ ሥርዓት ውስብስብ ብላ፤ እርስ በእርሷ እየተተረማመሰች ስትጫረስና የሰው ልጅ ደም ምድርን እንደ ደራሽ ውሃ ሲያጥለቀልቃት ተመልክቷት ልቡ ደነገጠ እጮኛው እንድትሆንም አስቀያሚ የፍቅር ደብዳቤ በሰው ልጅ ደም ጽፎ ልብ በጦር ሲወጋ ስሎ ከሙት ሙት የሬሳ አበባ ጋር ላከላት፡፡

ወሬውን ስሰማ ማመን ቢሳነኝ አምን ዘንድ መናፍስቱ የደብዳቤውን ግልባጭ ሰጠኝና ለእናንተም ላደርስ ወደድኩ፡፡ «ውድ የኔ ቆንጆ ሰላም ጤናና በረከት ካንቺ የራቀ እንዲሆን ሰይጣናዊ ምኞቴ ነው» ይላል ደብዳቤው በመግቢያው ጽሑፉ ቀጥሎ፤ «ምድር ሆይ ካየሁሽ ቀን ጀምሮ ነፍስ አልበላ ደም አልጠጣ ብሎኝ ክስት ብዬልሻለሁ፡፡ እንደው ብታይኝ በታሪክ የምታውቂኝ ሰይጣን አልመስልም፡፡ ሆዴ! ባንቺ የተነሳ አይናፋር ሆኜልሻለሁ፡፡ የእሽታ መልስሽን ዛሬ ነገ ሳትይ አሁኑኑ እንድትልኪልኝ አስጠንቀቅሻለሁ!!! እሺ ካልሽ በይኝ ካላልሽ ግን ወየውልሽ ይላል ደብዳቤው፡፡»

ሰይጣን ዓለምን ለማፍቀር ያነሳሳውን ነገር እንዲህ ገልጾ ነበር፡፡ ዓለም አለ ሰይጣን ስለ ዓለም ውበት ሲገልጽ አውሮፓ የተሰኘው ከእኔ ሌላ ላሳር የሚለው ፖለቲካ አቋም «ራሷ» ማረከኝ፣ አሜሪካ ብላ የጠራችው የግብረ ሰዶም አራማጅ «ደረቷ» ያጓጓል፣ ሩቅ ምሥራቅ የተሰኘው የጦር መሣሪያ በገፍ ማምረት «ዳሌዋ» እንቅልፍ አላስወስድ አለኝ፣ አፍሪካዊ ለተባለው የነጮችን መጤ ባህል ለሚያራምድ «ባቷ» ቃል የለኝም፡፡ ግን አለ ሰይጣን አንድ እንከን አግኝቶባት ኢትዮጵያ የተሰኘው ተረከዟ ውበቷን አጠፋው፡፡ የተረከዙ ባህሪ መቻቻል የሚሉት ቫይረስ አለበት፡፡ አንተ ትብስ አንቺ ትብሺ ተባብለን አብረን ከዓለም ጋር እንዳንኖር ይህ ለዘመናት አብሮ የቆየው የሕዝቦቿ የመቻቻል ባህርይን የሚበክል ቫይረስ በመካከላችን እየገባ እያበጣበጠንና እየናጠን ይገኛል ብሏል፡፡

ዓለም ደብዳቤው እንደደረሳት የእሽታ አጸፋዋን ብትመልስም ኢትዮጵያ ግን እጆቿን ወደ ፈጣሪዋ በመዘርጋት ስትቃወምና ለዚህ ተንኮሉ ቦታ እንደማትሰጠው ስትገልፅ እሱም ተናድዶባታል፡፡

 

አዲሱ ገረመው

Published in መዝናኛ
Friday, 06 October 2017 18:43

ሲኦል ለእድሳት ሊዘጋ ነው

 

ዓለም ዝም ያለው፣ ታላላቅ ኃያላን አገራት ሁሉ ፀጥ ብለው ተመልካች የሆኑበት አረመኔያዊውና እውነተኛ ትርኢት በጭራሽ አላባራም፡፡ እንዲያውም ብሶበታል፡፡ ሶሪያ ደበነች፤ ኢራቅን ፈጇት፤ ሊቢያን አናወዟት፤ ግብፆችን አረዱ፤ ኢትዮጵያውንኑ ወንድሞቻችን ደገሙ፤ ኮሪያ፣ አሜሪካ፣ ኤርትራ ብቻ ያልነካኩት የለም ግን ዝም ተብለዋል ሀይ ባይ አልተገኘም፡፡ ሰውን በጅምላ የሚጨርሱ ክፋት ከአቅም በላይ የሆነባቸውና ያናወዛቸው ግፈኞች ዛሬም ዓለምን በየአቅጣጫው እያተራመሱ ሰይጣናዊ ተልዕኳቸውን በመወጣት ሲኦልን እያስፋፉ ይገኛሉ፡፡

አንድ ቡድን ዓለምን ሲያስጨንቅ ዓለም መሪዎች ያጣች ይመስላል፡፡ ነገሩ ግራ የገባ ነው፡፡ ልምምዳቸው በሜዳ ነው፡፡ ይባስ ብለው ለዚሁ ሽብር ተግባር የሚጠቅሙ ሕፃናትን እያሳደጉ ነው፡፡ አልተሸሸጉም፡፡ ሆኖም ዝም ተብሏል፡፡

ይሄው እያደገ የሚሄደው አረመኔያዊ አገዳደል መልኩን ከእርድ ቀይሯል፡፡ በደማሚት፣ በእሳት፣ በውሃ መድፈቅ እንዲሁም ሰሞኑን በምድረ አሜሪካ እንኳን ሳይቀር በአውቶማቲክ መሣሪያ ጅምላ ጭፍጨፋው እየተደረገ ነው፡፡ ሰውን ሲገድል ብዙ ልቦችን እንደሚገድል ያውቃል፡፡ ከሚሞተው ሰው በላይ ቀሪውን የዓለም ሕዝብ ለማቃጠል፡፡ ሁሌ እያሰብን እየዘገነነን እንድንኖር እያደረገ ነው፡፡ ሀይ ባይ እስከሌለ ድረስ ገና ይቀጥል ይሆናል ማን ያውቃል፡፡

ይህንን ተግባር በተደጋጋሚ የተመለከተው ሳጥናኤልም አዲስ የማስፋፊያ ስልት በመቀየስ ሲኦልን አፍርሶ ለመገንባት ማሰቡን አስታውቋል፡፡ እንዴት ብላችሁ ለምትጠይቁ ብቻ መልሱን እነሆ፡፡

ሲኦልን ላልተወሰነ ጊዜ በእድሳት ምክንያት ልዘጋው ነው አለ የሲኦል ከንቲባ የተዋረድ እርኩስ ሳጥናኤል በቃል አቀባዮቹ አጋንንት አማካኝነት፡፡ የሰይጣን ቃል አቀባዮች እንደሚሉት ከሆነ የደንበኞች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየበዛ በመምጣቱ የተሻለ አሠራርን ለመቀየስ ስለፈለጉ ነው የማስፋፊያ ግንባታውን የሚያከናውኑት፡፡

ሲኦልን ለእድሳት ለመዝጋት ከመግለጼ በፊት መረጃዎችን በበርካታ ማስታወቂያ ቦርዶቼ፣ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች፤ እንዲሁም በጽህፈት ቤቶቼ በኩል እንዲተላለፍ አድርጌያለሁ ይለናል የተገኘው መረጃ፡፡

የማስታወቂያ ቦርድ የሚላቸው ለእርሱ ግብር ላደሩና የሰውን ደም በከንቱ የሚያፈሱ ቡድኖችን ሲሆን፤ ቆንስላ ጽህፈት ቤት የሚላቸው ደግሞ የራቁት ጭፈራ የሚካሄድባቸውን እንዲሁም ጽህፈት ቤቶች የሚላቸው መሰል አረመኔያዊና ሰይጣናዊ ድርጊት የሚካሄድባቸውን ስፍራዎች ነው፡፡

በግንባታው ወቅት ወደ ሲኦል ለሚገቡ ነፍሳትም ጊዜያዊ የሰፈራ መጠለያ የተዘጋጀላቸው ሲሆን ሲኦል ውስጥ ይሰጥ የነበረው አገልግሎት በስፍራው እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡

ግንባታው ሲፈጸም ሲኦል የመቀበል አቅሙን በእጥፍ እንደሚያሳድግ የተገለጸ ሲሆን፤ ጨለማው በፊት ከነበረው ጥቁር ወፍራም ጨለማ ሰባት እጥፍ እንደሚጠቁር ተገልጿል፡፡ የሚያቃጥለውም እሳት ምድር ከምናውቀው ፍም ከመሰለ ብረት ሰባት እጥፍ እንደሚቀላ ተነግሯል፡፡ ቲኬት የቆረጠች አንድ ኃጢአተኛ ነፍስን በካልቾ እየተቀባበሉ ወደ ሲኦል የሚያደርሷት እርኩሳን መናፍስት ለዚህ ሥራ መሳካት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በትጋት ይሰራሉ፡፡ ለቅልጥፍናቸውም አስተማማኝ የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ቃል አቀባዩ በቁጣ ተናግረዋል፡፡

ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስም ምድር ላይ ከሚገኙ ነፍስን እያደኑ ከሚገድሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ጋር እንደ እጅና ጓንት ሆነው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡ ለእድሳቱ የሚደረገው ወጪ ምን ያህል እንደሆነ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

እንግዲህ «ሞኝ ሲያወራ ብልህ አድምጥ» አይደል የሚባለው ነገሩ ፌዝ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን ዓለም ዛሬ ላይ እያስተናገደች ካለችው የመጥፎ ድርጊት እውነታዎች ጋር ሲነጻጸር ፍጻሜው ይህ ይመስላል፡፡ እንደ እኛ አገር ባሉ ቤተ እምነቶች መጥፎ ሥራን የሰራ የወደፊት ዕጣ ፈንታው መጥፎ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ታዲያ ይህንኑ ለማስገንዘብና ለመጥፎ ድርጊቶች እጆቻችን ተባባሪ እንዳይሆኑ ማስጠንቀቂያ ይሆነን ዘንድ የተዘጋጀ መልዕክት መሆኑንም ልብ ልንለው ይገባል፡፡

የተፈጠርነው በሕይወት መንገድ ላይ የበቀሉ አረሞችን እየነቀልን በነፃነት ለመኖር እንጂ ሕይወት ባበቀለቻቸው አረሞች ላይ ተጨማሪ ሙጃዎችን ለማብቀል አይደለም፡፡ እንደ ባህር ማዶ አረመኔዎች ሰውን በግፍ መግደል ደረጃ ላይ ባንደርስም እንኳን በጎን የምናደርጋቸው አሉታዊ ሥራችን ከእዛ የሚተናነሱ አይመስለኝም፡፡ ሀሜት፣ ጉቦ፣ የሀሰት ምስክርነት፣ ከባህል በማፈንገጥ ራቁት መሄድ ወዘተ... እንደ አገር የተወገዙ ድርጊቶችን ማከናወን በራሱ ወዴት እየሄድን ነው ያስብላል፡፡ ዓይንን መጥፎ ከማየት እጅን ለመጥፎ ድርጊት ከመዘርጋ፣ እግርን ወደ ክፉ ሥራ እንዳይሮጥ መከልከል ይኖርብናል፡፡ ያን ጊዜ ለሌላው ዓለም ምሳሌነታችን ይቀጥላል፡፡ የሲኦል እራትም አንሆንም፡፡

 

አዲሱ ገረመው

 

 

Published in መዝናኛ

የፈጠራው ባለቤት አቶ ካሳሁን ገረመው፤

 

ካሳሁን ገረመው ከዚህ ቀደም በመንገድ ትራንስፖረት ባለስልጣን የአሽከርካሪዎች ፈታኝ ቴክኒሻን ሆኖ ለ12 ዓመታት በሙያው ያገለገለ ትጉህ ባለሙያ ነው። በዚህ ሙያው ከሞተር ብስክሌት እስከ ከባድ መኪና የመፈተን እና የማሰልጠን ሥራንም ሲሰራ ቆይቷል።

ካሳሁን ለበርካታ ዓመታት በዚህ ሙያ ላይ ሲቆይ በዘርፉ ብቁ ያደረጉትን ልምዶች እና ተሞክሮዎችን ማዳበር ችያለሁ በማለት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ባደረገበት ወቅት አውግቶናል። አሁን ደግሞ እርሱ ተሰማርቶ ሲሰራበት በቆየበት የአሽከርካሪ ፈተና አሰጣጥ ሥርዓትን ያሻሽላል በማለት አንድ አዲስ «አነስተኛ የፈጠራ» ሥራን ይዞ ብቅ ብሏል። ይህን «ውህድ አነስተኛ የፈጠራ ሥራ» ለመስራት ያነሳሳውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚገኘውን የትራፊክ አደጋን ብቁ እና ኃላፊነት የሚሰማቸው አሽከርካሪዎችን በመፍጠር መቀነስ ይቻላል ብሎ በማሰቡ መሆኑን ይገልፃል።

«የትራፊክ አደጋ በምን ምክንያት እንደሚደርስ ማወቅ አስፈላጊ ነው። አደጋው ከመንገድ የጥራት ጉድለት፣ ከአሽከርካሪ ብቃት ማነስ፣ እንዲሁም በመሰል ችግሮች ሊከሰት ይችላል» የሚለው የፈጠራ ባለሙያው ከረጅም ዓመታት ልምዱ በመነሳት ሲገልፅ አብዛኛውን ጊዜ አደጋ የሚከሰተው እውቀት በጎደለው እና ንቁ ባልሆነ አሽከርካሪ እንደሆነ ይናገራል። ብቃት የጎደለው አሽከርካሪን ደግሞ ደካማ የምዘና እና የፈተና ሂደት ይፈጥረዋል ይላል። በተለይም ሂደቱ ለሙስና የተጋለጠ መሆኑ ችግሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል ይላል። አቶ ካሳሁን ከላይ ለተጠቀሰው ችግር ልምዴን ተጠቅሜ የፈተና ሥርዓቱን ውጤታማ የሚያደርግ አዲስ የፈጠራ ሥራ ይዤ ብቅ ብያለሁ ይላል። እኛም ይዘቱ ምን እንደሚመስል በዚህ መልክ አዘጋጅተን ቀርበናል።

«በአገራችን የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱ ፈታኝን እና ተፈታኝን በግል የሚያገናኝ ነው። ይህም ለአሠራር እና ለብቃት መመዘኛ መዳከም ክፍተት ይፈጥራል» የሚለው የፈጠራ ባለሙያ፤ እርሱ ከዚህ የተለየ አዲስ የፈተና ሥርዓት መፍጠሩን ይናገራል። ይህ አነስተኛ የፈጠራ ቴክኖሎጂ በርቀት የአሽከርካሪዎች የብቃት ማረጋገጫ የተግባር ፈተና የሚሰጥ ሲሆን፤ በተግባር መፈተኛ መኪናው ላይ እንደሚገጠም ይገልፃል። ለዚህም ዘመኑ የደረሰባቸውን ቴክኖሎጂዎች በማቀናጀት አንድ ወጥ የፈተና ሥርዓት ዘርግቷል። ማለትም ኤም...አር. (የርቀት የምስል መቅረጫ)፣ሲም ካርድ፣ የውስጥ ሴንሰር፣ካሜራዎች፣ የጂፒኤስ አንቴና፣ የ3ጂ እና 4ጂ አንቴና፣ ኮምፒውተር እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ ቴክኖሎ ጂዎችን በማቀናጀት ይህንን ዘመናዊ የአሽከርካሪ መፈተኛ ዘዴ መፍጠር ችሏል። አቶ ካሳሁን የዚህን አዲስ ዓይነት የፈተና መቆጣጠሪያ ዘዴ ጠቀሜታዎች በዚህ መልክ ያብራራዋል።

«አሽከርካሪው በፈተና ላይ በሚሆንበት ጊዜ ማንነቱን፣ አቀማመጡን፣ እይታውን፣ ስሜቱን፣ የእጅ እና የእግር እንቅስቃሴውን ብሎም የመቆጣጠሪያ መሣሪያ አጠቃቀሙን ማየት ይቻላል» በማለት በቀላሉ የተፈታኙን እንቅስቃሴ ከርቀት በኔትወርክ እና በተገጠሙለት መሣሪያዎች አማካኝነት መቆጣጠር እና ውጤቱን በግልፅ ማስቀመጥ እንደሚቻል ይናገራል። በፈተና ወቅት የተሽከርካ ሪውን ፍጥነት እንዲሁም አስፈላጊውን የማሽከርከር ሕግ እና ሥርዓት ተግባር ላይ እያዋለ መሆኑን ለመቆጣጠር ይህ አዲስ ፈጠራ ትልቅ እገዛ ያደርጋል። በተለያዩ መንገዶች እና የትራፊክ ሁኔታዎች ላይ የተሽከርካሪውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በቀጥታ በመከታተል ውጤት መስጠት ከማስቻሉም ባለፈ የመረጃ መያዣ ቋት ውስጥ በቀላሉ ለማስቀመጥ ቴክኖሎጂው ምቹ ነው።

«የትራፊክ አደጋ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ደርሷል። ችግሩ በስፋት የሚከሰተው ደግሞ በአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስ ነው» የሚለው የፈጠራ ባለሙያው፤ የእርሱን የፈጠራ ሥራ በዚህ የፈተና ሥርዓት ላይ መጠቀም ከተቻለ ብቃት ያላቸው አሽከርካሪዎችን ማውጣት እና አደጋውን መቀነስ እንደሚቻል ይናገራል። ይህን «ውህድ አነስተኛ የፈጠራ ሥራ» በአነስተኛ፣ መካከለኛ፣ በከባድ እንዲሁም በሌሎች ተሽከርካሪዎች ላይ መግጠም እንደሚቻልም ያስረዳል።

«ይህ የፈጠራ ሥራ ለየት የሚያደርገው በኔትወርክ አማካኝነት በሚተላለፍ ምስል ፈታኙ በርቀት ከከተማ ውጪም ሆኖ እንኳ ተፈታኙን መመዘን የሚችልበት እድል ይሰጣል» የሚለው አቶ ካሳሁን ይህ ደግሞ በሁሉም ክልሎች ያሉትን ተፈታኞች በአንድ ማእከል ለመፈተን የሚያስችል እንደሆነ ይገልፃል። በዚህም ሥነ ምግባርን የተከተለ፣ ኃላፊነት ያለው እና ከሙስና ፅዱ የሆነ የፈተና ሥርዓት መዘርጋት እንደሚቻል ይናገራል።

ካሳሁን በዚህ አነስተኛ የፈጠራ ሥራ ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የግልጋሎት ሞዴል ማረጋገጫ ሰርተፍኬት አግኝቷል። ቴክኖሎጂውን ለማስፋት እና የፈተና ሥርዓቱን እርሱ ባስተዋወቀው ቴክኖሎጂ ታግዞ እንዲሰጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረም ይገኛል። «ለመንገድ ትራንስፖርት ባስተዋወቅኩት አዲስ ቴክኖሎጂ ታግዤ ፈተናው እንዴት ተግባር ላይ እንደሚውል ለማሳየት ሞክሬያለሁ» የሚለው የፈጠራ ባለሙያው ቴክኖሎጂውን የተመለከቱት አካላት በሥራው ቢያምኑበትም አንዳንድ የአፈፃፀም ጉዳዮች ላይ ገና መግባባት ላይ እንዳልደረሱ ይገልፃል። እርሱ ባለው አቅም ይህን የፈጠራ ሥራ ቢያስተዋውቅም የሚመለከተው አካል ተግባራዊነቱ ላይ በንቃት አብሮት ሊሰራ እና ሊደግፈው እንደሚገባም ይናገራል። ከመረጃ ማጠራቀሚያ ቋት ግንባታ አኳያ ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር መግባባት ላይ እንዳልደረሱ እና ግንባታውን በራሱ ማድረግ እንደሚኖርበት እንደገለፁለት ይናገራል። ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች ይህን ቋት በራሱ መገንባት እንደማይችልና የተቋሙ የራሱ ቋት ሊኖረው እንደሚገባና ጉዳዩ ሳይቋጭ በእንጥልጥል እንደቆመም ያስረዳል። ይህን የመፈተኛ ቴክኖሎጂ በአንድ መኪና ላይ ለመግጠም በትንሹ 23ሺ ብር እንደሚፈጅም ገልጿል።

«ግልፅ እና አስተማማኝ የመፈተኛ መሣሪያ ፈጥሬያለሁ» የሚለው አቶ ካሳሁን የሚመለከተው አካል ይህን መገንዘብ ይኖበታል የሚል እሳቤን ያንፀባርቃል። አሽከርካሪዎች ብቁ ካልሆኑ አደጋ እንደሚያደርሱ ይታወቃል። በመሆኑም እነዚህን አሽከርካሪዎች ተቆጣጥሮ እና መዝኖ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ የሚሰጣቸው አካል የመመዘኛውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ይኖርበታል። በቴክኖሎጂ የታገዘ የፈተና ሥርዓት ደግሞ ለምዘናው ትክክለኝነት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው፤ ይህን መሰል የፈጠራ ሥራ ባለሙያዎች ይዘው ሲቀርቡ ተግባራዊ ማድረጉ መልካም እንደሆነ ያስረዳል።

«የትራፊክ አደጋን መቀነስ የሁላችንም ኃላፊነት ነው» የሚለው የፈጠራ ባለሙያው በትራንስፖርት ዘርፍ ከትራፊክ አደጋ ውጪ በርካታ ችግሮች እንደሚስተዋሉና የመንገድ መጨናነቅን ጨምሮ ለትራፊክ እንቅስቃሴ እንቅፋት የሚሆኑ በርከት ያሉ ችግሮች መኖራቸውን ያስረዳል። በመሆኑም ሁሉም ያለውን ክህሎት ተጠቅሞ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር ከቻለ ችግሩን በትብብር መቅረፍ እና ሰላማዊ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር ምክንያት መሆን ይቻላል ሲል መልዕክቱን ያስተላልፋል።

የዝግጅት ከፍላችን በተለያየ ጊዜ የፈጠራ ባለሙያዎችን በማነጋገር ሥራዎቻቸውን ያቀርባል። አብዛኞቹ እንደ ችግር የሚያነሱት ጉዳይ ዘርፉን ማነቃቃት የሚችሉ አካላት፤ ማለትም መንግሥት፣ ባለሀብቶች እና ሌሎች ተቋማት ቴክኖሎጂዎቹ ተግባር ላይ ውለው ለማህበረሰቡ እሴት እንዲጨምሩ ድጋፍ ለማድረግ ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ነው። ይህ ደግሞ የፈጠራ ባለሙያው ተስፋ እንዲቆርጥ እና ለተሻለ ሥራ እንዳይነሳሳ የሚያደርግ ነው። የዝግጅት ክፍላችን እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት አካላት ዘርፉን ማነቃቃት እና መደገፍ ይኖርባቸዋል የሚል እምነት አለው። አንድ የፈጠራ ባለሙያን ስንደግፍ በርካታ ችግሮችን እየቀረፍን እና ሕይወትን ቀላል እያደረግን እንደምንሄድ ሁላችንም መገንዘብ ይኖርብናል። ሰላም!

 

ዳግም ከበደ

ካሳሁን ገረመው ከዚህ ቀደም በመንገድ ትራንስፖረት ባለስልጣን የአሽከርካሪዎች ፈታኝ ቴክኒሻን ሆኖ ለ12 ዓመታት በሙያው ያገለገለ ትጉህ ባለሙያ ነው። በዚህ ሙያው ከሞተር ብስክሌት እስከ ከባድ መኪና የመፈተን እና የማሰልጠን ሥራንም ሲሰራ ቆይቷል።

ካሳሁን ለበርካታ ዓመታት በዚህ ሙያ ላይ ሲቆይ በዘርፉ ብቁ ያደረጉትን ልምዶች እና ተሞክሮዎችን ማዳበር ችያለሁ በማለት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ባደረገበት ወቅት አውግቶናል። አሁን ደግሞ እርሱ ተሰማርቶ ሲሰራበት በቆየበት የአሽከርካሪ ፈተና አሰጣጥ ሥርዓትን ያሻሽላል በማለት አንድ አዲስ «አነስተኛ የፈጠራ» ሥራን ይዞ ብቅ ብሏል። ይህን «ውህድ አነስተኛ የፈጠራ ሥራ» ለመስራት ያነሳሳውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚገኘውን የትራፊክ አደጋን ብቁ እና ኃላፊነት የሚሰማቸው አሽከርካሪዎችን በመፍጠር መቀነስ ይቻላል ብሎ በማሰቡ መሆኑን ይገልፃል።

«የትራፊክ አደጋ በምን ምክንያት እንደሚደርስ ማወቅ አስፈላጊ ነው። አደጋው ከመንገድ የጥራት ጉድለት፣ ከአሽከርካሪ ብቃት ማነስ፣ እንዲሁም በመሰል ችግሮች ሊከሰት ይችላል» የሚለው የፈጠራ ባለሙያው ከረጅም ዓመታት ልምዱ በመነሳት ሲገልፅ አብዛኛውን ጊዜ አደጋ የሚከሰተው እውቀት በጎደለው እና ንቁ ባልሆነ አሽከርካሪ እንደሆነ ይናገራል። ብቃት የጎደለው አሽከርካሪን ደግሞ ደካማ የምዘና እና የፈተና ሂደት ይፈጥረዋል ይላል። በተለይም ሂደቱ ለሙስና የተጋለጠ መሆኑ ችግሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል ይላል። አቶ ካሳሁን ከላይ ለተጠቀሰው ችግር ልምዴን ተጠቅሜ የፈተና ሥርዓቱን ውጤታማ የሚያደርግ አዲስ የፈጠራ ሥራ ይዤ ብቅ ብያለሁ ይላል። እኛም ይዘቱ ምን እንደሚመስል በዚህ መልክ አዘጋጅተን ቀርበናል።

«በአገራችን የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱ ፈታኝን እና ተፈታኝን በግል የሚያገናኝ ነው። ይህም ለአሠራር እና ለብቃት መመዘኛ መዳከም ክፍተት ይፈጥራል» የሚለው የፈጠራ ባለሙያ፤ እርሱ ከዚህ የተለየ አዲስ የፈተና ሥርዓት መፍጠሩን ይናገራል። ይህ አነስተኛ የፈጠራ ቴክኖሎጂ በርቀት የአሽከርካሪዎች የብቃት ማረጋገጫ የተግባር ፈተና የሚሰጥ ሲሆን፤ በተግባር መፈተኛ መኪናው ላይ እንደሚገጠም ይገልፃል። ለዚህም ዘመኑ የደረሰባቸውን ቴክኖሎጂዎች በማቀናጀት አንድ ወጥ የፈተና ሥርዓት ዘርግቷል። ማለትም ኤም...አር. (የርቀት የምስል መቅረጫ)፣ሲም ካርድ፣ የውስጥ ሴንሰር፣ካሜራዎች፣ የጂፒኤስ አንቴና፣ የ3ጂ እና 4ጂ አንቴና፣ ኮምፒውተር እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ ቴክኖሎ ጂዎችን በማቀናጀት ይህንን ዘመናዊ የአሽከርካሪ መፈተኛ ዘዴ መፍጠር ችሏል። አቶ ካሳሁን የዚህን አዲስ ዓይነት የፈተና መቆጣጠሪያ ዘዴ ጠቀሜታዎች በዚህ መልክ ያብራራዋል።

«አሽከርካሪው በፈተና ላይ በሚሆንበት ጊዜ ማንነቱን፣ አቀማመጡን፣ እይታውን፣ ስሜቱን፣ የእጅ እና የእግር እንቅስቃሴውን ብሎም የመቆጣጠሪያ መሣሪያ አጠቃቀሙን ማየት ይቻላል» በማለት በቀላሉ የተፈታኙን እንቅስቃሴ ከርቀት በኔትወርክ እና በተገጠሙለት መሣሪያዎች አማካኝነት መቆጣጠር እና ውጤቱን በግልፅ ማስቀመጥ እንደሚቻል ይናገራል። በፈተና ወቅት የተሽከርካ ሪውን ፍጥነት እንዲሁም አስፈላጊውን የማሽከርከር ሕግ እና ሥርዓት ተግባር ላይ እያዋለ መሆኑን ለመቆጣጠር ይህ አዲስ ፈጠራ ትልቅ እገዛ ያደርጋል። በተለያዩ መንገዶች እና የትራፊክ ሁኔታዎች ላይ የተሽከርካሪውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በቀጥታ በመከታተል ውጤት መስጠት ከማስቻሉም ባለፈ የመረጃ መያዣ ቋት ውስጥ በቀላሉ ለማስቀመጥ ቴክኖሎጂው ምቹ ነው።

«የትራፊክ አደጋ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ደርሷል። ችግሩ በስፋት የሚከሰተው ደግሞ በአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስ ነው» የሚለው የፈጠራ ባለሙያው፤ የእርሱን የፈጠራ ሥራ በዚህ የፈተና ሥርዓት ላይ መጠቀም ከተቻለ ብቃት ያላቸው አሽከርካሪዎችን ማውጣት እና አደጋውን መቀነስ እንደሚቻል ይናገራል። ይህን «ውህድ አነስተኛ የፈጠራ ሥራ» በአነስተኛ፣ መካከለኛ፣ በከባድ እንዲሁም በሌሎች ተሽከርካሪዎች ላይ መግጠም እንደሚቻልም ያስረዳል።

«ይህ የፈጠራ ሥራ ለየት የሚያደርገው በኔትወርክ አማካኝነት በሚተላለፍ ምስል ፈታኙ በርቀት ከከተማ ውጪም ሆኖ እንኳ ተፈታኙን መመዘን የሚችልበት እድል ይሰጣል» የሚለው አቶ ካሳሁን ይህ ደግሞ በሁሉም ክልሎች ያሉትን ተፈታኞች በአንድ ማእከል ለመፈተን የሚያስችል እንደሆነ ይገልፃል። በዚህም ሥነ ምግባርን የተከተለ፣ ኃላፊነት ያለው እና ከሙስና ፅዱ የሆነ የፈተና ሥርዓት መዘርጋት እንደሚቻል ይናገራል።

ካሳሁን በዚህ አነስተኛ የፈጠራ ሥራ ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የግልጋሎት ሞዴል ማረጋገጫ ሰርተፍኬት አግኝቷል። ቴክኖሎጂውን ለማስፋት እና የፈተና ሥርዓቱን እርሱ ባስተዋወቀው ቴክኖሎጂ ታግዞ እንዲሰጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረም ይገኛል። «ለመንገድ ትራንስፖርት ባስተዋወቅኩት አዲስ ቴክኖሎጂ ታግዤ ፈተናው እንዴት ተግባር ላይ እንደሚውል ለማሳየት ሞክሬያለሁ» የሚለው የፈጠራ ባለሙያው ቴክኖሎጂውን የተመለከቱት አካላት በሥራው ቢያምኑበትም አንዳንድ የአፈፃፀም ጉዳዮች ላይ ገና መግባባት ላይ እንዳልደረሱ ይገልፃል። እርሱ ባለው አቅም ይህን የፈጠራ ሥራ ቢያስተዋውቅም የሚመለከተው አካል ተግባራዊነቱ ላይ በንቃት አብሮት ሊሰራ እና ሊደግፈው እንደሚገባም ይናገራል። ከመረጃ ማጠራቀሚያ ቋት ግንባታ አኳያ ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር መግባባት ላይ እንዳልደረሱ እና ግንባታውን በራሱ ማድረግ እንደሚኖርበት እንደገለፁለት ይናገራል። ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች ይህን ቋት በራሱ መገንባት እንደማይችልና የተቋሙ የራሱ ቋት ሊኖረው እንደሚገባና ጉዳዩ ሳይቋጭ በእንጥልጥል እንደቆመም ያስረዳል። ይህን የመፈተኛ ቴክኖሎጂ በአንድ መኪና ላይ ለመግጠም በትንሹ 23ሺ ብር እንደሚፈጅም ገልጿል።

«ግልፅ እና አስተማማኝ የመፈተኛ መሣሪያ ፈጥሬያለሁ» የሚለው አቶ ካሳሁን የሚመለከተው አካል ይህን መገንዘብ ይኖበታል የሚል እሳቤን ያንፀባርቃል። አሽከርካሪዎች ብቁ ካልሆኑ አደጋ እንደሚያደርሱ ይታወቃል። በመሆኑም እነዚህን አሽከርካሪዎች ተቆጣጥሮ እና መዝኖ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ የሚሰጣቸው አካል የመመዘኛውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ይኖርበታል። በቴክኖሎጂ የታገዘ የፈተና ሥርዓት ደግሞ ለምዘናው ትክክለኝነት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው፤ ይህን መሰል የፈጠራ ሥራ ባለሙያዎች ይዘው ሲቀርቡ ተግባራዊ ማድረጉ መልካም እንደሆነ ያስረዳል።

«የትራፊክ አደጋን መቀነስ የሁላችንም ኃላፊነት ነው» የሚለው የፈጠራ ባለሙያው በትራንስፖርት ዘርፍ ከትራፊክ አደጋ ውጪ በርካታ ችግሮች እንደሚስተዋሉና የመንገድ መጨናነቅን ጨምሮ ለትራፊክ እንቅስቃሴ እንቅፋት የሚሆኑ በርከት ያሉ ችግሮች መኖራቸውን ያስረዳል። በመሆኑም ሁሉም ያለውን ክህሎት ተጠቅሞ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር ከቻለ ችግሩን በትብብር መቅረፍ እና ሰላማዊ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር ምክንያት መሆን ይቻላል ሲል መልዕክቱን ያስተላልፋል።

የዝግጅት ከፍላችን በተለያየ ጊዜ የፈጠራ ባለሙያዎችን በማነጋገር ሥራዎቻቸውን ያቀርባል። አብዛኞቹ እንደ ችግር የሚያነሱት ጉዳይ ዘርፉን ማነቃቃት የሚችሉ አካላት፤ ማለትም መንግሥት፣ ባለሀብቶች እና ሌሎች ተቋማት ቴክኖሎጂዎቹ ተግባር ላይ ውለው ለማህበረሰቡ እሴት እንዲጨምሩ ድጋፍ ለማድረግ ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ነው። ይህ ደግሞ የፈጠራ ባለሙያው ተስፋ እንዲቆርጥ እና ለተሻለ ሥራ እንዳይነሳሳ የሚያደርግ ነው። የዝግጅት ክፍላችን እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት አካላት ዘርፉን ማነቃቃት እና መደገፍ ይኖርባቸዋል የሚል እምነት አለው። አንድ የፈጠራ ባለሙያን ስንደግፍ በርካታ ችግሮችን እየቀረፍን እና ሕይወትን ቀላል እያደረግን እንደምንሄድ ሁላችንም መገንዘብ ይኖርብናል። ሰላም!

 

ዳግም ከበደ

Published in ማህበራዊ

አመልካቾች፡- እነ አቶ በቀለ ከበደ

ተጠሪ ፡-አቶ ብዙነህ መሸሻ

ጉዳዩ በሽያጭ ምክንያት ተከፈለ የተባለ ገንዘብ ይመለስልኝ ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን፤ ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ በአሁኑ አመልካቾች ላይ በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው፡፡ የክሱ ይዘትም፡- አመልካቾች ከመኖሪያ ቤታቸውና ከይዞታቸው በመቀነስ በግምት 270 .ሜትር የሆነና ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤት በብር 40,000 (አርባ ሺህ) ሸጠውላቸው ብር 10,000 (አስር ሺህ) በውሉ ዕለት የከፈሏቸው መሆኑን ብር 20,000 (ሃያ ሺህ ብር) ደግሞ አመልካቾች ቤቱን አድሰው ለተጠሪ ሲያስረክቡ እንዲከፈላቸው የተስማሙ ቢሆንም አመልካቾች ቤቱን ባለማደሳቸው ተጠሪ በራሳቸው ገንዘብ እንዲያድሱ ስምምነት ላይ በመደረሱ ምክንያት ተጠሪ ብር 20,000 (ሃያ ሺህ ብር) ወጪ በማድረግ ቤቱን አድሰው የተረከቡ መሆኑን ከዚህም በተጨማሪ ተጠሪ ብር 51,000 (ሃምሳ አንድ ሺህ ብር) ወጪ በማድረግ ደረጃውን የጠበቀ አምስት ክፍል ቤት የሰሩ መሆኑን ተጠሪ በአመልካች ላይ የቤት ሽያጭ ውሉን በውልና ማስረጃ ጽ/ቤት ቀርበው እንዲያስ መዘግቡ በፍርድ ቤት ክስ መስርተው ክርክሩ ሲካሄድ ቆይቶ ፍርድ ቤት በሕግ ፊት የሚፀና ውል የለም በማለት ውሳኔ መስጠቱን በመዘርዘር በማይጸና ውል የተወሰደውና ለግንባታ የወጣው ወጪ በድምሩ ብር 81,000 (ሰማንያ አንድ ሺህ ብር) እንዲከፍሏቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአሁኑ አመልካቾች በበኩላቸው ተጠሪ ወደ ቤቱ የገቡት በኃይል መሆኑን በተጨማሪነት የገነቡት ግንባታም አለመኖሩን ገልፀው ይኸው ገንዘብ ተከፍሏቸው ግራ ቀኙ ወደነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ ሊደረግ ይገባል ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም አመልካቾች ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን ገንዘብ ለተጠሪ ሊከፍሉ ይገባል? ወይስ አይገባም? የሚለውንና ተያያዥ ጭብጦችን በመያዝ የግራ ቀኙን ክርክርና ምስክሮችን ቃል መርምሮ አመልካቾች ለተጠሪ ብር 61,000 ውሳኔ ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ከሚታሰብ ሕጋዊ ወለድ ጋር ሊከፍሉ ይገባል በማለት ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ አመልካቾች ባለመስማማት ይግባኛቸውን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ፀንቷል፡፡

አመልካቾች በተጻፈ የሰበር አቤቱታ በበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሠረት የሆነ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል የሚሉባቸውን ምክንያቶች ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ፡- የቦታ ሽያጭ ስለመኖሩ በሕግ መሠረት በጽሑፍ የተደረገና በሚመለታቸው የመንግሥት አካላት ፊት የተፈረመ የቤት ሽያጭ ውል በሌለበት ሁኔታ ለቤቱ እድሳት የወጣ ገንዘብ ለተጠሪ ሊመለስላቸው ይገባል መባሉ እንዲሁም ተጠሪ ተጨማሪ ግንባታ አከናወንኩ የሚል ክርክር ሳይኖራቸውና በማስረጃም ባልተደገፈበት መንገድ ለብር 61,000 (ስልሳ አንድ ሺህ ብር) ኃላፊ ተደርገን ውሳኔ መስጠቱ ያለግባብ ስለሆነ ሊታረም የሚገባው ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታቸው ተመርምሮም በማይፀና ረቂቅ ውል አመልካቾች የተቀበሉትን ብር 10,000 እንዲመልሱ ከመደረጉ በተጨማሪ ተጠሪ የግንባታ ወጪ እንዲከፍሉ የመወሰኑን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ለሰበር ችሎቱ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው ግራ ቀኙ በጽሑፍ ተከራክረዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተመለከተው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ ምርመራውም አመልካቾች ለተጠሪ ገንዘቡን እንዲመልሱ ተብሎ የተወሰነው በሕጉ ተቀባይነት ያለውን ማስረጃ መሠረት ባደረገ መንገድ ነው? ወይስ አይደለም? የሚል ነው፡፡

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪ በአመልካቾች ላይ ክስ የመሰረቱት አመልካቾች ቤት ሸጠውልኝ የተወሰነ ገንዘብ ከፍዬአለሁ የተወሰነውንም የአመልካቾችን ግዴታ ለመወጣት ስል ወል አድርጌ ቤቱን በመረከብ ተጨማሪ ግንባታ አከናውኜ ባለበት ሁኔታ በፍርድ ቤት በተደረገው ክርክር በሕግ ፊት የሚጸና ውል የለም ስለተባለ ገንዘቡ ሊመለስልኝ ይገባል በማለት መሆኑን በግራ ቀኙ መካከል የቤት ሽያጭ ውል አለ፣ የለም የሚለው ክርክርም በፍርድ ቤት ታይቶ ሕጋዊ የሆነ የቤት ሽያጭ ውል የሌለ መሆኑ መረጋገጡን ነው፡፡

የቤት ሽያጭ ውል የሌለ መሆኑ የተረጋገጠው ተጠሪ አመልካቾች የቤት ሽያጭ ውሉን ውል አዋዋይ ፊት ቀርበው ሊያስመዘግቡልኝ ይገባል በማለት በመሠረቱት ክስ አመልካቾች በሕግ ፊት የሚጸና ውል የለም በማለት በመከራከራቸው ምክንያት መሆኑንም ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ ችለናል፡፡ ተጠሪ ለአሁኑ የሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነውን ጉዳይ ያቀረቡትም የቤት ሽያጭ ውል የለም ተብሎ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ሲሆን፤ አመልካቾች ገንዘቡን ስለመቀበላቸው ያቀረቡትና ያሰሙት ማስረጃ የሰው ምስክሮችንና የሰነድ ማስረጃ ነው፡፡ አመልካቾችም የሰው ምስክሮችን አቅርበው ያሰሙ መሆኑን የስር ፍርድ ቤት የውሳኔ ግልባጭ ያሳያል፡፡ የስር ፍርድ ቤት አመልካቾችን ለክሱ ኃላፊ ያደረገው ገንዘቡን ከተጠሪ ስለመቀበላቸው ተጠሪ በተገቢው ማስረጃ አስረድተዋል፡፡ አመልካች ግን በምስክሮቻቸው ሊያስተባብሉ አልቻሉም በሚል ምክንያት ነው፡፡ እንግዲህ ከላይ የተመለከቱት ነጥቦች በስር ፍርድ ቤት የተረጋገጡት ሲሆን፤ አመልካች የስር ፍርድ ቤት የሥነ ሥርዓት ግድፈት ፈጽሟል በማለት የሚያቀርቡት አንዱ ነጥብ ተጠሪ ሕጋዊ የሆነ የቤት ሽያጭ ውል አለ በማለት ያቀረቡት ክርክር ተቀባይነት ሳያገኝ በቤት ሽያጭ ውል የተከፈለው ገንዘብ እንዲመለስ ተብሎ መወሰኑ ለጉዳዩ መቅረብ ከሚገባው ማስረጃ ዓይነት አንፃር ተገቢነት የሌለው ነው በማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የቤት ሽያጭ ውልን አስመልክቶ ክርክሩ የቀረበበት አግባብ በተጠሪ በኩል የቀረበው የቤት ሽያጭ ውል በውል አዋዋይ ፊት እንዲመዘገብ የሚል ክስ በመቅረቡ በመሆኑና በሕጉ አግባብ የተደረገ የቤት ሽያጭ ውል የለም ተብሎ ድምዳሜ የተደረሰ በመሆኑ ተጠሪ በሽያጩ ምክንያት ለአመልካቾች የሰጡትን ገንዘብ ሊመለስልኝ ይገባል በማለት ጥያቄ ከማቅረብና በማናቸውም ማስረጃ ከማስረዳት የማይከለክል መሆኑን ከፍ///ቁጥር 1808/2/18152001 እስከ 2019 እንዲሁም ከፍ///ቁጥር 2162 እና 2164 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የቀረበውን የማስረጃ ዓይነት መሠረት በማድረግ መቃወሚያ የሚቀርብበት ጉዳይ አይደለም፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ አመልካቾች ያቀረቡት ክርክር ተቀባይነት ያለው ሆኖ አላገኘነውም፡፡

አመልካቾች አጥብቀው የሚከራከሩትና በዚህ ሰበር ችሎት እንዲታይ የተያዘው ጭብጥ በጉዳዩ ላይ የቀረበው ማስረጃ በሕጉ ስላለው ተቀባይነት ነው፡፡ ተጠሪ ሕጋዊ አይደለም በተባለው የቤት ሽያጭ ውል መሠረት ለአመልካቾች ከፍያለሁ የሚሉት የገንዘብ መጠን ብር 10,000 (አስር ሺህ ብር) ሲሆን፤ ሌላው ብር 51,000 ከቤቱ ርክክብ በኋላ ለተደረገ ግንባታ የወጣ ወጪ ነው፡፡ አመልካቾች ለጉዳዩ የቀረበው ማስረጃ ተቀባይነት የሌለው ነው የሚሉት ይህንኑ የገንዘብ መጠን በሰው ማስረጃ ሊረጋገጥ አይገባም፤ ተጠሪ በማስረጃም ክርክራቸውን አላስደገፉም በማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአመልካችና የተጠሪ ግንኙነት የብድር ውል ሳይሆን ሕጋዊ ያልሆነ የቤት ሽያጭ ውል ስለመሆኑ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ በሰው ምስክር ሊረጋገጥ አይገባም ተብሎ በአመልካቾች የቀረበው ክርክርም ሆነ ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት በጭብጥነት የተያዘው ነጥብ የ////ቁጥር 2472 ለጉዳዩ አግባብነት የሌለው በመሆኑ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ ጉዳዩ መገዛት ያለበት ስለሽያጭ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች በተለይ በመመልከት ወይም ስለጠቅላላው ውል የተመለከቱትን ድንጋጌዎች በማየት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ለጉዳዩ ቀጥተኛ ተፈጻሚነት ያላቸው ድንጋጌዎች በጠቅላላው የውል ሕግ ሲሆን፤ በዚህ የውል ሕግ አንድን ነገር ለመግዛት ገንዘቡን የከፈለ ሰው ግዢው ሕጋዊ አይደለም ተብሎ ውሳኔ ከተሰጠው ገንዘቡ እንዲመለስለት ጥያቄ ያቀርብና ክሱን በሰው ምስክር ቢያስረዳ የሰው ምስክሮች ቃል ተቀባይነት የለውም ሊባል እንደማይችል ከ////ቁጥር 2001 እስከ 2019 ድረስ የተመለከቱት ድንጋጌዎች ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም የስር ፍርድ ቤት ተጠሪ ያቀረቧቸውን የሰው ምስክሮች ቃል በመቀበል ውሳኔ መስጠቱ ከላይ ከተመለከቱት የጠቅላላ ውል ሕግ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ አንፃር ሕጋዊ እንጂ የሚነቀፍ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ተጠሪ በቦታው ላይ ግንባታውን ያከናወኑት በአመልካቾች በኩል ተቃውሞ እየቀረበ ባለበት ሁኔታ ስለመሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ ያልተረጋገጠ ሲሆን፤ የግንባታ ፈቃድ ሳያወጡ ግንባታው መከናወኑ ከ////ቁጥር 1178 እና 1179 ድንጋጌዎች አንፃር ሲታይ የተጠሪን የግንባታ ወጪ ይተካልኝ ጥያቄን ሕጋዊ አይደለም ለማለት የሚያስችል አይሆንም፡፡ በአጠቃላይ በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የሌለበት ሆኖ አግኝተናል፡፡ በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

ውሳኔ

1. በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ በፍ////ሕ ቁጥር 348/1/መሠረት ፀንቷል፡፡

2. በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሣራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

አያሌው ንጉሴ

 

Published in ፖለቲካ

 

ኢትዮጵያን በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ እውቅና እንዲቸራት ካደረጉ በርካታ መገለጫዎች መካከል በዓለም ዙሪያ በተወዳጅ መጠጥነቱ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ቡና አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ አገሪቱ አረቢካ የተባለውን ዝርያ ጨምሮ የበርካታ የቡና ዝርያዎች መገኛ ናት፡፡

ቡና አብቃይ የሆኑ የዓለም አገራትን በሚያካልለውና በተለምዶ የቡና ቀጣና (Coffee Belt) ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ላይ አተኩሮ ጥናት የሚያደርገው cornerofthecafe.com ድረ-ገፅ ኢትዮጵያንና ቡናዋን «የቡና መገኛ፣ የተለያዩ የቡና ዝርያዎችን ማብቀል የምትችል አገር፣ የዚችን አገር ቡና በትክክል ለመግለፅ የሚያስችል ቃል ማግኘት አስቸጋሪ ነው» በማለት ይገልፃል፡፡

ትኩረታቸውን በቡና ላይ አድርገው የሚሰሩ ተቋማት መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ቡና የዓለማችን ቀዳሚው ተወዳጅ መጠጥ ነው፡፡ ወይን፣ ቢራና ሌሎች የአልኮል መጠጦችን የሚያዘወትረው የዓለማችን ሰው ቁጥሩ ቢደመር እንኳ ቡና ከሚጠጣው ሰው ብዛት ያነሰ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በምድሪቱ ላይ በየቀኑ ሁለት ቢሊዮን ስኒ ቡና እንደሚጠጣና ዓለም አቀፉ የቡና ኢንዱስትሪም በዓመት ከ100 ቢሊዮን ዩሮ የበለጠ ገንዘብ እንደሚያንቀሳቅስ መረጃዎቹ ይጠቁማሉ፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቦ ከሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ባሻገር በአገር ውስጥ ያለው የገበያ ድርሻም ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህም በላይ በቡና እርሻና በንግድ ሥራ የተሰማሩ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎችም የህልውናቸው መሠረት በመሆኑ ፋይዳው እጅግ የላቀ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ካሉ 437 ቡና ላኪዎች ውስጥ 120 ያህሉ 90 በመቶ የሚሆነውን ቡና ወደ ውጭ የሚልኩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተሞክሮ ብንመለከት እንኳ፣ 100 ሚሊዮን የሚሆኑ የታዳጊ አገራት ዜጎች ኑሮ በቡናና ቡና ነክ ሥራዎች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን መረጃ እንደሚያሳየው፣ በ1994 .ም የነበረው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የቡና ምርት መጠን 126188 ቶን ነበር፡፡ በወቅቱ ለውጭ ገበያ ይቀርብ የነበረው የምርት መጠንም 110347 ቶን ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የአንድ ቶን ቡና አማካይ ዋጋም 1472 ዶላር ነበር፡፡

አገሪቱ በቡና ሀብታቸው ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ከሆኑ የፕላኔታችን አገራት መካከል አንዷ በመሆኗ ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ባከናወናቻቸው ተግባራት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተመዘገበው ዓመታዊ የቡና ምርት መጠን 225494 ቶን ሲሆን፣ ከምርቱ የተገኘው ገቢ ደግሞ 882 ሚሊዮን ዶላር ሆኗል፡፡

አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ካከናወናቻቸው ተግባራት መካከል ዘርፉን ለይቶ የሚመራ ተቋም ማቋቋሟ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶችን ከመደገፍ ባለፈ ምርታማነት ለማሳደግ በትኩረት እንዲሰራ ኃላፊነት ተሰጥቶት የተቋቋመው መንግሥታዊ ተቋም ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን ነው፡፡

ባለስልጣኑ በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ዘመናዊ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት በማረጋገጥ የኢኮኖሚ እድገቱ የሚጠይቀውን የውጭ ምንዛሪ የማመንጨትና በንዑስ ዘርፉ የሚሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ገቢና ኑሮ በመሠረታዊነት የመለወጥ ተልዕኮ አንግቦ በአዲስ መልኩ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 364/2008 የተደራጀ መስሪያ ቤት ነው፡፡

በመንግሥት የተሰጠውን ኃላፊነት ከመወጣት አንፃርም፣ በ2009 በጀት ዓመት ካከናወናቸው ተግባራት መካከል ቁልፍ ተግባራት ብለው የተለዩት ዋና ዋና ክንውኖችን በመጥቀስ ማሳየት ይገባል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ያሉበትን ችግሮች በመለየት ተገቢው የአሠራርና የአደረጃጀት ሥርዓት ተዘርግቷል፤ በክልል ከተሞች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የዘርፉ ተግዳሮቶች/ማነቆዎች ተለይተዋል፤ የቡና ግብይት፣ ጥራትና ቁጥጥር አዋጅ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ፀድቋል፤ ከቡና ምርት የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል ተብሎ የታመነበትን የቡና ምርምር ኢንስቲትዩት ለማቋቋም ደንብ ተዘጋጅቷል፤ የቡና ጥራት መቆጣጠሪያ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪም፣ የቡና ምርታማነትና ጥራት ማሻሻያ ፓኬጅ ተዘጋጅቶ እስከ ወረዳ ላሉ ባለድርሻ አካላት ስልጠና ተሰጥቷል፤ ፓኬጁ ታትሞም ተዘጋጅቷል፡፡

2009 በጀት ዓመት 668 ሺ ስምንት ቶን እሸት ቡና (የዕቅዱን 99 በመቶ) እና 414 336 ቶን ጀንፈል ቡና (የእቅዱን 93 በመቶ) በመጀመሪያ ደረጃ የግብይት ማዕከላት ለገበያ ቀርቧል፡፡ አፈፃፀሙ ከ2008 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ፣ በእሸት ቡና የ193 550 ቶን (40 በመቶ) እና በጀንፈል ቡና 102 746 ቶን (33 በመቶ) ጭማሪ አሳይቷል፡፡ አፈፃፀሙም 83.46 በመቶ ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ ከሁሉም ቡና አምራች ክልሎች (ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ከጋምቤላና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች) 305 284.47 ቶን ቡና ወደ ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች የመጋዘን አገልግሎት ተሸኝቷል/ተልኳል፡፡ ከዚህም ውስጥ 124 304.93 ቶን ያህሉ የታጠበ ሲሆን፣ 181 174.34 ቶኑ ደግሞ ያልታጠበ ቡና ነው፡፡ ከሁሉም ቡና አምራች ክልሎች ከፍ ያለ መጠን ያለው ቡና ያቀረበው ክልል ደግሞ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ 241ሺ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ 941 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ 225494 ቶን ቡና በማቅረብ 882 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል፡፡ ይህም የእቅዱን 94 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ ያሳያል፡፡ በ2008 በጀት ዓመት 198 501 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቦ 722 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ይታወሳል፡፡ የ2009ኙ አፈፃፀም ከ2008ቱ ጋር ሲነፃፀር፣ በአቅርቦት የ26993 ቶን (14 በመቶ)፣ በገቢ ደግሞ የ60 ሚሊዮን ዶላር (22 በመቶ) ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ጀርመን (16 በመቶ)፣ ሳዑዲ አረቢያ (15 በመቶ)፣ አሜሪካ (9 በመቶ)፣ ጃፓን፣ ቤልጂየም፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ኢጣሊያ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ሱዳን ለውጭ ገበያ የቀረበው ቡና መዳረሻ የሆኑ የመጀመሪያዎቹ 10 ሀገራት ሲሆኑ፣ እነዚህ አገራት 86 በመቶ የሚሆነውን የመጠን እና 85 በመቶ የሚሆነውን የገቢ ድርሻ ይሸፍናሉ፡፡

2009 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበው ቡና የሲዳማ፣ የነቀምቴ፣ የጅማ፣ የይርጋጨፌ፣ የሊሙና የሐረር ቡና ከፍተኛ ድርሻ ነበራቸው፡፡ ከእነዚህ አካባቢዎች የተገኘው የቡና ምርት ለውጭ ገበያ ከቀረበው አጠቃላይ ምርት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን አቅርቦት ይይዛል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ለውጭ ገበያ ቀርቦ ከተገኘው አጠቃላይ ገቢም መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ገቢ የተገኘው ከእነዚህ አካባቢዎች በቀረበው ምርት አማካኝነት ነው፡፡

ከዋጋ አንጻር፣ በ2009 የአስሩ ዋና ዋና መዳረሻ አገራት አማካይ ዋጋ በቶን 3866 ዶላር የነበረ ሲሆን በ2008 በጀት ዓመት ከነበረው ዋጋ በቶን 3526 ዶላር ጋር ሲነጻጸር በቶን የ340 ዶላር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በዚህም ከአስሩ ዋና ዋና የቡና ተቀባይ አገራት የተገኘው ገቢ ጭማሪ የታየበት ሲሆን ሳዑዲ አረቢያ ከፍተኛውን ድርሻ ይዛለች፡፡

የገበያ ማስተዋወቅና ትስስር ተግባራትን ከማጠ ናከርና ከማስፋፋት አንፃር ደግሞ በጃፓን፣ በአሜሪካ ሲያትል፣ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በተካሄደው 15ኛው የአፍሪካ የቡና ኮንፈረንስና ኤግዚቢሽን፣ በዱባይ፣ በሃንጋሪ፣ በሴኔጋል፣ በቻይና እንዲሁም በሕንድ በተካሄዱ የቡና፣ የሻይና የቅመማ ቅመም ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ኤክስፖ ላይ በመሳተፍ ምርት የማስተዋወቅ፣ አዳዲስ ገዥዎችን የማፍራትና ውል የመዋዋል ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ የቡና ምርት አቅራቢ ከሆኑት የኦሮሚያና የደቡብ፣ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 1710.363 ቶን ቡና ተወርሶ 38.7 ሚሊዮን ብር ለክልሎቹ ገቢ ሆኗል፡፡

ከዚህ ባሻገርም፣ ባለፈው የበጀት ዓመት የተገኙትን ውጤቶች አጠናክሮ ለማስቀጠል የ2010 የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡ ከእነዚህ አቅጣጫዎች መካከልም፣ በአመለካከት፣ በክህሎት፣ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይልና በአገልግሎት አሰጣጥ ብቁ የሆነ ተቋም መፍጠር፣ ቅንጅታዊ አሠራርን ማሳደግ፣ ዘመናዊ፣ ሕጋዊና ፍትሃዊ የግብይት ሥርዓት በመገንባትና የገበያ ማስፋፊያ ሥራዎችን በማከናወን የወጪ ንግድ እንዲጨምር ማስቻል፤ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርትና ምርታማነት ማሳደግ፤ የኤክስቴንሽን ተደራሽነትና ጥራት፣ የቴክኖሎጂ ብዜትና ስርጭት እንዲሁም ተባይና በሽታን መከላከልና መቆጣጠር ይጠቀሳሉ፡፡

ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት በመገንባት ለልማትም ሆነ ለግብይት በላቀ ደረጃ መጠቀም እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና የኪራይ ሰብሳቢነት ማነቆዎችን ትርጉም ባለው ደረጃ ማስወገድ እንዲሁም የኅብረተሰብ በተለይም የሴቶችና የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥም የትኩረት አቅጣጫዎቹ አካል ናቸው፡፡

 

አንተነህ ቸሬ

 

 

Published in ኢኮኖሚ

የኢራን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሮሃኒ (በስተግራ) እና የቱርክ አቻቸው ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን

 

የኢራኑ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሮሃኒ እና የቱርኩ አቻቸው ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን የኢራቅ ኩርዶች ባለፈው ወር ያካሄዱትን ውሳኔ-ሕዝብ እንደማይቀበሉት በጋራ አሳውቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን ለጉብኝት ከሄዱበት ቴህራን ሆነው ከኢራኑ አቻቸው ሐሰን ሮሃኒ ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ የኩርድ ክልላዊ መንግሥት (Kurdish Regional Government - KRG) ከኢራቅ ለመገንጠል ለሞከረበት ውሳኔ-ሕዝብ ተገቢ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ወሳኝ የሆኑ የመፍትሄ እርምጃዎች ይወሰዳሉ ብለው የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ እርምጃዎቹ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ግን በግልፅ የሰጡት ፍንጭ አለመኖሩም ተዘግቧል፡፡

..አ መስከረም 25 ቀን 2017 የተካሄደውን ውሳኔ-ሕዝብ ተከትሎ የኩርድ ክልላዊ መንግሥት የሚገኝበትንና ቱርክ ከኢራቅ ጋር የምትዋሰንበትን ድንበር ልትዘጋ እንደምትችል አስጠንቅቃ ነበር፡፡ ኤርዶጋን ከሮሃኒ ጋር ሆነው በሰጡት መግለጫም የኩርድ ክልላዊ መንግሥትን አብጠልጥለውታል፡፡ «ምን ዓይነት ውሳኔ ነው ያካሄዱት? ውሳኔ-ሕዝብ የተባለው ነገር ሕገ-ወጥና ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ነው፤ ውጤቱንም አንቀበለውም፤ ለዚህ ውሳኔ ከእሥራኤል ውጪ ድጋፍና እውቅና የሰጠ አካል የለም» ብለዋል፡፡

«የኩርድ ክልላዊ መንግሥት ከእሥራኤሉ የስለላ ድርጅት (ሞሳድ) ጋር ተባብሮ በሰራው ሥራ ውሳኔ-ሕዝቡን ሕጋዊ ማድረግ አይችልም» በማለት በእሥራኤል ላይ የሚሰነዝሩትን የተለመደ ወቀሳቸው ንና ክሳቸውን አሰምተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ ኢራቅና ሶርያ የተደቀነባቸው የመከፋፈል አደጋ ሊያስከትልባቸው የሚችለውን ጫና ለመቋቋም የሚያስችል መላ ለመፈለግ ሀገራቸው ከኢራን ጋር እንደተስማማችም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም፣ በአሁኑ ወቅት በኢራንና በቱርክ መካከል ያለውን የ10 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ልውውጥ ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግና ሀገራቱ በኃይል ዘርፍ ያላቸውን ትብብርም ለማሳደግ እንዳቀዱም ገልጸዋል፡፡ ሁለቱም ሀገራት የየራሳቸውን የመገበያያ ገንዘቦች በመጠቀም የንግድ ልውውጥ ለማድረግ የሚስችላቸውን አሠራር እንደሚዘረጉም አስታውቀዋል፡፡

ምንም እንኳ ሁለቱ ሀገራት በሶርያ የእርስ በእርስ ጦርነት በተለያየ ጎራ የተሰለፉ ኃይሎችን እየደገፉ ቢሆንም፣ የእርስ በእርስ ጦርነቱ እየተካሄደባት ባለችው ሶርያ ውስጥ ነፃ ቀጣናዎች እንዲመሰረቱ የሚያስች ለውን የአስታናውን ስምምነት (Astana Deal) ለመተግበር የሚያግዙ ተግባራዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ በጋራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

የኢራኑ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሮሃኒ በበኩላቸው የኢራቅን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል የመከፋፈል ተግባርን እንደሚያወግዙ ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህ ተግባራት መካከል ከኢራቅ የተነጠለ የኩርድ መንግሥት አንዱ እንደሆነ በመጠቆም፡፡

«ጉዳዩ በቀጥታ እኛን ስለሚመለከተን አሁን ለምናውቃት ኢራቅ አዲስ ካርታ የሚሰጥ ተግባርን እንቃወማለን፤ ይሁን እንጂ የኢራቅ ኩርዶች መልካም ጎረቤቶቻችንና ወዳጆቻችን ናቸው፤ ከማንም ወገን ግፊት እንዲደርስባቸው አንፈልግም» በማለት የኩርድ ክልላዊ መንግሥት ባለሥልጣናት ውሳኔ-ሕዝቡ እንዲካሄድ ግፊት ማድረግ እንዳልነበረባቸው አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ የኢራቅ ኩርዶች ከኢራቅ ለመነጠል የያዙት ሃሳብና ያካሄዱት ውሳኔ ሕዝብ የውጭ ኃይሎች ሴራ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ የኩርድ ክልላዊ መንግሥት ውሳኔ-ሕዝብን አጥብቀው ሲቃወሙ ነበር፡፡ ኩርዶች ድምፃቸውን እየሰጡ በነበረበት ወቅት እንኳ፣ ኤርዶጋን አካባቢውን በምጣኔ ሀብት ቀውስ ሊያሽመደምዱት እንዳቀዱ መዛታቸው ይታወሳል፡፡

የውሳኔ-ሕዝቡ ውጤት እንደታወቀም ቱርክና ኢራቅ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ከማድረጋቸው በተጨማሪ፣ ኢራቅ ከኢራን ጋር የጦር ልምምድ እንደምታደርግ አስታውቃ ነበር፡፡ ቱርክና ኢራን ግን የጋራ የጦር ልምምድ ለማድረግ እስካሁን ስምምነት ላይ ስለመድረሳቸው የተባለ ነገር አለመኖሩ ተዘግቧል፡፡ ይሁን እንጂ የቱርክ ጦር አዛዥ ጀኔራል ሁሉሲ አካር ሰሞኑን ኢራንን ጎብኝተዋል፡፡ ጉብኝቱም ከ1979ኙ የኢራን እስላማዊ አብዮት ወዲህ የመጀመሪያው እንደሆነና በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ትብብር ጠንከር እያለ መምጣቱን አመላካች ነው ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል ባለፈው ነሐሴ ወር የኢራን ጦር አዛዥ ሜጀር ጀኔራል መሐመድ ሑሴን ባሄሪ አንካራን ሲጎበኙ ከ1979ኙ የኢራን እስላማዊ አብዮት ወዲህ ቱርክን የጎበኙ የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣን ሆነው ነበር፡፡

..አ መስከረም 25 ቀን 2017 ከፊል ራስ ገዝ በሆነውና በሰሜናዊ ኢራቅ በሚገኘው የኩርድ ክልላዊ መንግሥት በተካሄደው ውሳኔ-ሕዝብ፣ ድምፅ ከሰጠው ሕዝብ/መራጭ ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ኩርዶች ከኢራቅ ማዕከላዊ መንግሥት ተነጥለው የራሳቸውን መንግሥትና ሀገር እንዲመሰርቱ ለሚያቀነቅነው ጎራ ድጋፉን መግለፁ/ድምፅ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

ውሳኔ-ሕዝቡ የኢራቅ ማዕከላዊ መንግሥትና የኩርድ ከፊል ራስ ገዝ ክልላዊ መንግሥት በድንበር/ግዛት በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ሳይቀር ተካሂዶ ነበር፡፡ ከእነዚህ አካባቢዎች መካከል በነዳጅ ሀብቷ የበለፀገችው የኪርኩክ ከተማ አንዷ እንደነበረች የሚታወስ ነው፡፡

ውሳኔ-ሕዝቡን ተከትሎም የኢራቅ መንግሥት ውሳኔ-ሕዝቡንም ሆነ የውሳኔውን ውጤት እንደማይቀበል ገልፆ ነበር፡፡ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይደር አል-አባዲ ውሳኔ-ሕዝቡ ተቀባይነት እንደሌለው በመግለፅ የኩርድ ክልላዊ መንግሥት የሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት በሚፈቅደው አሠራር መሠረት ለድርድር እንዲዘጋጅ አሳስበው ነበር፡፡

አካባቢውን ከአሸባሪው አይ.ኤስ.አይ.ኤስ. (ISIS) ቁጥጥር ነፃ ለማውጣት በሚደረገው ዘመቻ የኩርድ ኃይሎች (ፔሽመርጋዎች) ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የኩርድ ኃይሎች ባሳዩት ተጋድሎ ምስጋናውን የቸራቸው ቢሆንም፣ ላካሄዱት የመገንጠል ውሳኔ-ሕዝብ ግን የጠበቁትን ድጋፍ ሳይሰጣቸው ቀርቷል፡፡

አብዛኞቹ የኢራቅ ጎረቤቶች በበኩላቸው «ድርጊቱ ቀጣናውን የበለጠ አደጋ ውስጥ ሊከተው ይችላል» በማለት ውሳኔ-ሕዝቡን እንደተቃወሙት ይታወሳል፡፡ የግብፅና የዮርዳኖስ አየር መንገዶችን ጨምሮ ሌሎች የበርካታ ሀገራት ዓለም አቀፍ አየር መንገዶችም ወደ ኩርድ ክልል የሚያደርጓቸውን በረራዎች ለመሰረዝ እንደሚገደዱም አስታውቀው ነበር፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አሜሪካና ብሪታኒያም በበኩላቸው ውሳኔ-ሕዝቡ ዓለም አቀፉን አሸባሪ ቡድን አይ.ኤስ.አይ.ኤስ. (ISIS)ን ለመዋጋትና በሶርያ የሚካሄደውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማብረድ የሚደረገውን ዘመቻና ጥረት ይጎዳል በሚል አመክንዮ ውሳኔ-ሕዝቡን መቃወማቸው የሚታወስ ነው፡፡

የኩርድ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት መሱድ ባርዛኒ በበኩላቸው፣ የውሳኔ-ሕዝቡን የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት አድንቀው፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኩርዶችን መብትና ፍላጎት እንዲያከብር ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡

የውሳኔ-ሕዝቡ ውጤት ይፋ እንደተደረገም ኩርዶች ደስታቸውን በአደባባይ ይገልፃሉ ተብሎ ቢጠበቅም የኧርቢል አደባባይ ፀጥ ረጭ ብሎ መታየቱ ዓለምን አስገርሟል፡፡ ኩርዶች ደስታቸውን ሳይገልፁ የቀሩትም ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ለውሳኔ-ሕዝቡ የሰጠው ምላሽና የኢራቅ ማዕከላዊ መንግሥት የኃይል እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ፍንጭ በመስጠቱ ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት በበለኩሉ፣ ሁሉም ወገኖች ጉዳዩን በሰላማዊ ውይይትና በድርድር እንዲፈቱት ጥሪውን አቅርቦ ነበር፡፡ ኅብረቱ ባወጣው መግለጫ፣ የኢራቅ መንግሥትና የኩርድ ክልላዊ መንግሥት ባለስልጣናት ጉዳዩን ለመፍታት ሰላማዊና የሰከነ ንግግር እንዲያደርጉ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡

ከቀጣናው ሀገራት መካከል ለውሳኔ-ሕዝቡ ድጋፏን የሰጠችው ሀገር እሥራኤል ብቻ ናት፡፡ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፣ «ውሳኔው ኩርዶች የራሳቸውን ነፃ መንግሥት ለመመስረት ጥረታቸውን ያሳዩበት ሕጋዊ እርምጃቸው ነው» በማለት ለሰሜናዊ ኢራቅ ነዋሪዎቹ ድርጊት እውቅናና ድጋፍ ችረውታል፡፡

ቁጥራቸው ከ30 ሚሊዮን እንደሚልቅ የሚነገርላቸው ኩርዶች፣ በኢራቅ፣ በኢራን፣ በቱርክና በሶርያ ተበታትነው ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ ሀገራት የሚገኙ ኩርዶች ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል የዘለቁ ብሔራዊ የነፃነት ትግሎች ቢያደርጉም እስካሁን የራሳቸውን ነፃ ሀገር ለመመስረት አልቻሉም፡፡

(የመረጃው ምንጭ፡- አልጀዚራ ነው)

 

አንተነህ ቸሬ

Published in ዓለም አቀፍ

 

የቃላት ጦርነትና እሰጥ አገባ ከርሮ ሲያበቃና ሲበጠስ ነው አገራት ወደ ጦርነት ውስጥ የሚገቡት፡፡ ለዚህም ይመስላል የቻይናው ኮሚኒስት መሪ የነበሩት ማኦ ዜዱንግ ጦርነት የፖለቲካ ትግሉ በሌላ መልኩ ቀጣይነት ነው ያሉት፡፡ ማህበራዊ ድረገጾች ከፍተኛ የሃሳብ ፍልሚያ የሚካሄድባቸው ከጦርነት ያልተናነሱ አውድማዎች ናቸው፡፡ የማህበራዊው ሚዲያ ጥይት ባይጮህበትም ከመድፍና ታንክ በላይ በሰው ሕሊና ውስጥ የሚያጓራ ከሚሳይልም በላይ ተምዘግዝጎ የሚወነጨፍ፣ አናዋጭ፤ በስሜታዊነት የሚነዳ ለጥፋትም የሚያነሳሳ ነው፡፡ ፌስቡክ የሃሳብ ፍልሚያና ግብግብ የሚካሄድበት ጎራ መሆኑ በጀ እንጂ ሌላማ ቢሆን የከፋ እልቂትና ውድመት ሊያመጣ ይችል የነበረ የዘመኑ መገናኛ ብዙኃን ነው፡፡

ዛሬ ላይ ዓለምን ለጦርነት ስጋት እየጋበዛት ያለው በሚዲያ አማካኝነት የሚካሄደው ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ሥራና የቃላት ፍልሚያ ነው፡፡ ሃሳብን በሃሳብነቱ በሰላም፣ በሥርዓትና በጨዋነት መንገድ መግለጽ ይቻላል፡፡ የፌስ ቡክ ቀጣና ግን ሕግና ሥርዓት የለውም፡፡ ልቅነት፣ መረንነትና ሥርዓተ አልበኝነት ሞልቶ የነገሰበት፣ እያንዳንዱ በራሱ ዓለም ንጉሥ የሆነበት፣ የወደደውን የሚክብበት፣ የጠላውን ደግሞ የሚያጠለሽበት ነው፡፡ ዙሪያውን የተጠመደ ፈንጂ ያለ ይመስል በአንዲት ቃል ወይንም ሐረግ የተነሳ ሁሉም ቦታ መልኩን ቀይሮ ፍንዳታ በፍንዳታ ይሆናል፡፡

ማህበራዊ ድረ ገጽ አዲሱ ዓይነት ሚዲያ ሲሆን በአብዛኛው በአንድ ጉዳይ ላይ የተዛቡና ስሜትን የሚለዋውጡ መረጃዎች በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመርኩዘው ሆነ በፈጠራና በሀሰት የሚሰራጩበት ነው፡፡ ጥላቻን በስፋት የሚያሰራጭ፣ የተሳሳተ መረጃዎችንም ጭምር የማስረጽ ፍጥነቱ በሰከንዶች ዓለምን መድረስ የሚችል ነው፡፡

በፌስቡክ ዘመቻዎች በአጭር ቃላት የገዘፈ ስሜትን የሚያደፈርስ መልዕክት፤ ክብረ-ነክ የሆኑ የሀሰት ስም ማጥፋት፤ አስነዋሪ ስድብ እንደ ወረደ የሚስተናገድበትም ነው፡፡ ለማንበብ ለሕሊናም ሰቅጣጭና ዘግናኝ የሚሆንበትም አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ አንድ ሰው የሚሰጠውን የመነሻ ሃሳብ ምክንያት በማድረግ ሺህ ትርጉም የሚመነዘርበት፤ ቀና ትርጉም የሌለበት፤ ሁሉም ያሻውን የሚፈላሰ ፍበት፣ የሚያላግጥበት፣ የስድብ ሱስና አራራውን የሚወጣበት፣ የአስተያየት ሰጪው ተክለ ሰውነትና ስብዕናው ምን እንደሚመስል ጭምር በገሀድ የሚታይበት ውስጣዊ የባሕርይ ገመናን በአደባባይ በግላጭ አግጥጦና አፍጥጦ እንዲወጣ የሚያደርግ ነው ፌስቡክ፡፡

ማህበራዊ ድረገጾች በበለጸጉት አገራት የስለላ ተቋሞቻቸው ሰፊ የመረጃ ምንጭ ሲሆኑ በፈለጉት መንገድ ከየትኛውም ግለሰብ የታሪክ ቋት ውስጥ ጭምር መረጃ የሚሰበስቡበት ነው፡፡ በተለይም አሸባሪዎችን ለመከታተል ይጠቀሙበታል፡፡

ማህበራዊ ድረገጾች ለትምህርት፣ ለእውቀት፣ ለጥናትና ምርምር፣ ለታሪክ፣ ለትኩስ ዓለም አቀፍ ዜናዎች ወዘተ...ፈጣን መረጃዎችን ስለሚሰጡ የበለጠ እውቀት ለማግኘት ጠቀሜታቸው የጎላ ነው፡፡ በእነዚህ ማህበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት በቀላሉ በሚፈልጉት ርዕስ ዙሪያ ሰፊና የተለያዩ መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል፡፡

ድረ-ገፆቹ ጠቀሜታቸው የጎላ የመሆኑን ያህል አውዳሚና አጥፊ ጎንም አላቸው፡፡ በተለይ ወጣቱ ትውልድ የወሲብ አፍቃሪና ሰለባ እንዲሆን በማድረግ ተተኪውን ትውልድ ወደጥፋት እንዲምዘገዘግ ያደርጉታል፡፡

በዓለማችን ላይ አንድ ሰው ማወቅ ስለሚፈ ልገው ጉዳይ ኢንተርኔት ውስጥ ገብቶ በጎግል ወይንም በያሁ ፍለጋ ማከናወን ብቻ ነው የሚጠበ ቅበት፡፡ በአሁኑ ሰዓት ኢንተርኔት (በተለይም ማህበራዊ ሚዲያዎች) ዓለምን ልክ እንደ አንድ መንደር አቀራርበውታል፤ይሁን እንጂ፣ የዚያኑም ያህል አደጋነታቸው እየጎላ መጥቷል፡፡

ፌስቡክን በመሳሰሉ ድረገጾች የእውነተኛም ሆነ የሀሰተኛ ዜና ስርጭቱ የፈጠነና የገዘፈ ነው፡፡ የጥፋት መልዕክቶችን በማስተላለፍ፣ ጥላቻ በመዝራት፣ ስም በማጥፋት፣ ሕዝብን ከሕዝብ የማጋጨቱም ሥራ እንዲሁ ፈጣን ነው፡፡ ለበጎ ሥራዎችና ተግባራትም በብዙ መልኩ ይውላል፡፡ አጠቃቀሙ ከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ ግለሰቡ እንዲሰማው ከማድረግ ጀምሮ ጥንቃቄንም ይጠይቃል፡፡

ወደእኛ የፌስቡክ አጠቃቀም ታሪክ ስንመለስ በተለይ የሃሳብ ልዩነቶችን በማክበር የተለየ የሚባልን ሃሳብ ሥርዓት ባለው መልኩ የሚገልጹበት ሳይሆን ፖለቲካዊ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ጥላቻ፣ ስድብ፣ የማናቆርና ሕዝብን ከሕዝብ የማባላት መረንና ልቅ የወጡ ከጨዋነት በእጅጉ የራቁ ዘለፋዎችና ስድቦች፣ በስፋት የሚጻፉበትና የሚስተናገዱበት መድረክ ነው።

ልክ እንደ ክረምቱ በረዶና ጎርፍ፤ በፌስቡክ የአሉባልታና የስድብ ጋጋታ ይዘንባል፡፡ ከግለሰብ አልፈው ተርፈው ዘር እስከመስደብ ድረስ የተረማመዱ ዋልጌዎች የሚገኙበት መንደር ነው ፌስቡክ፡፡ ጎራው ሲታይ በመንግሥት ደጋፊዎችና በተቃዋሚው የተከፈለ ይመስላል፡፡ እውነቱ ግን ይህን የተንቀለቀለ እሳት በኢትዮጵያውያን ስም እየተጠቀመ የሚያቀጣጥለው ትልቁን የማባላትና የማናከስ ሥራ እየሰራ ያለው የኤርትራ መንግሥት የደህንነት ተቋም ነው፡፡

ይህ ምስጢር ያልገባቸው ኢትዮጵያውያን ደግሞ ጎሳዬ ዛሬ ተሰደበ በሚል የለየለት የስድብ ጦርነት ውስጥ በመግባት አንዱ አደኛውን ሲሰድብና ሲያንቋሽሽ ይውላል፤ ይህ እጅግ የተለመደ ሆኗል፡፡ ተከባብሮ የኖረን ሕዝብ በዚህ መልኩ ማናከስ ማባላት ለሀገራችን በፍጹም አይጠቅማትም፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አካሄድ መላቀቅ በመከባበር ሃሳብን መግለጽንና ምክንያታዊነትን መከተል መልካም ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብም የራሳችን አኩሪ ባሕልና ጨዋነት ያለን ነን፡፡ በሥርዓቱ በመናገርና በማስረዳት የሃሳብ ልዩነትን ማንጸባረቅ ይቻላል፡፡ ስድብ ተወልዶ ያደገበት የተመነደገበትም አገር የሆንን ያህል የአስጸያፊ ስድቦች ብቸኛ ባለቤቶች ሆነናል፡፡ የስድብ ፋብሪካ ወደ መሆን የተሸጋገሩትም ብዙ ናቸው፡፡ ቀጣዩና ተተኪው ትውልድ ከዚህ ምን ይማራል? ቢባል መልሱ ምንም ነው፡፡

ፌስቡክም ሆነ ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች በሌሎች ዓለማት እንደሚታየው ሁሉ ይልቁንም ለሀገርና ለሕዝብ ሰላምና አብሮነት የሚበጁ፤ ከስህተቶች መታረሚያ መውጫ መንገዶችን የሚያሳዩ፤ የድንቅ ሃሳቦች ማንሸራሸሪያ መድረኮች በመሆን ሲያገለግሉ ይታያሉ።

ፌስቡክ ሲታሰብ በዚህ መልኩ ምን ዓይነት ትውልድና ኅብረተሰብ እየተገነባ ነው? የሚለውም ጥያቄ በእጅጉ ያሳስባል፡፡ የመንግሥት ደጋፊ ነኝ የሚለውም ሆነ ተቃዋሚው በስድብ፣ በዘለፋ በስም ማጥፋት አልፎም ሕዝብን እስከመዝለፍና መስደብ ድረስ የተረማመዱ የተሸጋገሩ ጸያፍ ምልልሶችን በማድረግ ተጠምደዋል፡፡ ግለሰቦችንና ሕዝብን ያለመለየት ችግር ከባድ መዘዝን ያስከትላል፡፡ መላውን ሕዝብ መስደብ በምን መስፈርት እንደሚቻል ለማሰብ ይከብዳል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያው ጨርቁን ጥሎ አብዷል እየተባለ ያለውም በዚህና በዚሁ አሳሳቢ ጉዳይ ምክንያት ነው፡፡

ለራስም ሆነ ለሀገር የሚበጅ ሥራ በሚሰራበት ሰዓት መሽቶ እስኪነጋ ነግቶም እስኪመሽ ድረስ የጥላቻ ዘገሩን እየነቀነቀ ፌስ ቡክ ላይ ተጥዶ አፉን አሞጥሙጦ ስድብ ሲያዘንብ አንዱ ሌላውን ጥላሸት ሲቀባ ውሎ ያድራል፡፡ መቼም ጤነኛ የሆነ ሰው ያስበዋል ወይንም ያደርገዋል። ታዲያ ይሄ የጤና ነው ያስብላልን?

በፖለቲካው ጎራም ፌስቡክ የስድብ፣ የአሉባልታ የወረደ ተራ ወሬ መናኸሪያ የጥላቻ መስበኪያ ሕዝብን መንቀፊያ መስደቢያ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ጥያቄው በዚህ መልኩ በስድብ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት በአገር ደረጃ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ይቻላል ወይ የሚለው ነው፡፡ ይህ መንገድ የባሰ መተናነቅን የባሰ ጥላቻን የመጠፋፋት አቅጣጫን ይበልጥ እያሰፋ መቻቻልና መከባበር መደማመጥ የሚለውን እየናደና እያወደመ አገሪቷን ወደማይፈለግ የጥፋት አቅጣጫና እልቂት ከመምራት ውጪ አገራዊ ሰላምና መረጋጋትን አይፈጥርም፤ ይህን ሁሉም ልብ ሊለው ይገባል።

ይህ እንዲሆን ችግር እንዲፈጠር ማህበራዊ ሚዲያውን ተጠቅመው ሕዝብን ከሕዝብ የማናቆር፣ የማባላት፣ የማለያየት፣ አንዱ ብሔር በሌላው ላይ እንዲነሳ ግጭት እንዲፈጠር፣ ሰላም እንዲደፈርስ፣ በአጠቃላይ አገሪቷ የቀውስ ማዕበል ውስጥ እንድትወድቅ ቀን ከሌሊት የሚሰሩ እንቅልፍ አጥተው የሚንቀሳቀሱ ልማትና እድገታችንን የማይፈልጉ ጠላቶች እንዳሉን ሁሉም ሊያውቀው ይገባል፡፡

በግብጽና በኤርትራ የደህንነት ኃይሎችና ቁጥጥር ስር ሆነው በኢትዮጵያዊነት ስም እየተጠቀሙ በፌስ ቡክ አካውንታቸው ከፍተኛ የማባላት ሥራ የሚሰሩ፣ የመንግሥት ደጋፊ መስለው ሕዝብን ከሕዝብ በማናከስ ሥራ የተጠመዱ፣ በጠባብነት በትምክሕት የአስተሳሰብ ባርነት ውስጥ የሚዋኙ እንዳሉም ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ጊዜው አርቆ ማስተዋልን፣ ስለሀገርና ስለሕዝብ ሲባል ችግሮችን ሁሉ በመደማመጥና በመከባበር ልዩነትን በልዩነት ይዞ በጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ መቆምን የሚጠይቅ ነው፡፡

በፌስቡክ መንደር ውስጥ መሽገው የሚንከላ ወሱ ከእኛ በላይ አዋቂ የለም ለማለት የሚዳዳቸው፤ አስተሳሰበ ደካማዎች የሚጽፉትንና የሚለጥፉትን ተጠንቅቀው ለማስተዋል ቢችሉ በአገርና በሕዝብ ላይ ችግር ከመፍጠር ቢቆጠቡ ሃሳቦችን በጨዋ መልኩ ቢገልጹ ተጠቃሚው ሕዝብም መንግሥትም ነው፡፡ ከስድብና ከጥላቻ ፖለቲካ የሚገኝ ትምህርትም ሆነ ትርፍ የለም፡፡

«አላዋቂ ሳሚ ምን... ይለቀልቃልሆነና ትናንሽ አስተሳሰብ ያላቸው ፍጡራን ስለትልቋና በታሪክ ውስጥ ስለከበረችው፣ ዛሬም ወደትልቅነት እንደገና በመረማመድ ላይ ስላለችው፣ በዓለማችን የሰው ዘር መፍለቂያና መገኛ ታላላቅ በዓለም ደረጃ የተመዘገቡ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቶች፤ የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት፤ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችም እናት የሆነችውን አገር ሕዝቡን እርስ በእርሱ አባልተው ሊያፋጁት በዚህ ትርምስ መሀልም ለኢትዮጵያ ጠላቶች መጠቀሚያ መሣሪያ ሆነው አገር ለማጥፋት ሲክለፈለፉ ማየት የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡

ያላወቁት ትልቅ ነጥብ በየትኛውም የታሪክ ወቅት ጥንትም ዛሬም አገሩን ከየትኛውም ዓይነት ሴራና ደባ ጠብቆ አንድነቷ ሳይፈርስና ሳይናጋ ያኖራት ሕዝቡ መሆኑን ነው፡፡ የፌስቡክ አርበኞች በወሬና በስድብ የሚጋጭ፣ የሚባላ፣ በአሉባልታ ለዘመናት የኖረና ዛሬም ድረስ የዘለቀ አንድነቱን የሚያፈርስ አገሩን ለውጭ ጠላቶች መፈንጪያነት አሳልፎ የሚሰጥ ሕዝብ እንዳልሆነ፤ ይልቁንም ሳይለያይ አብሮነቱንና አንድነቱን ጠብቆና አጽንቶ የሚዘልቅ ብዝሀነቱ ውበቱና ድምቀቱ እንጂ የመለያያ ነጥቡ እንደማይሆን ወደ ኋላ ሄደው ታሪክን ቢፈትሹ ይመረጣል፡፡

 

መዝገቡ ዋኘው

 

 

Published in አጀንዳ

 

«እኔ ፌስ ቡክን የምጠቀመው ጀግንነትን ማሳያ ስለሆነ አይደለም፡፡ የምጠቀመው ሕዝብ ብዙ ሃሳብ አግኝቶ የተሻለውን እንዲመርጥ ለማድረግ ነው፡፡ ይህን ስል የልማት እቅድ አቅጄ ልማት ለማምጣት አይደለም፡፡ ልማት ለማምጣት የተግባር ሥራ ያስፈልጋል፡፡ በተግባር ለአገሬ የበኩሌን አደርጋለሁ፤እያደረኩም ነው፡፡ ፌስ ቡክ ላይ ግን አስተሳሰብን መገንባት ነው.........» የሚል ጽሑፍ አነበብኩ ይህ ጽሑፍ ከጅምሩ ጥሩ የመንደርደሪያ ሃሳብ ይዞ ተነስቶ የጀመረውን በጎ ሃሳብ ጥሎ የራሱን የፌስ ቡክ የጀግንነት ውሎ ሊያሳይ ሞከረ፡፡

የፌስ ቡክ ጀግኖች ቀድሞውንስ ሃሳብን አካፍሎ በምክንያት አሳምኖ መርታትን የጀግንነት መሠረት መች አደረጉት! የእነርሱ ጀግንነት ያለው ብሔርን ከብሔር፣ ሕዝብን ከሕዝብ፣ አገርን ከአገራት ጋር ማጋጨት፣ መንግሥትን ማብጠልጠል፣ ወደቀ ሲሉዋቸው ተሰበረ፤ ማለት እንጂ! መች ሀቅን ለመረጃ ፈላጊው ኅብረተሰብ ማድረስ ሆነ !

የአስተሳሰብ መገንቢያ የሆነውን ማህበራዊ ሚዲያ የሕዝብ ለሕዝብ ቂም መያያዣ፣ የአገር ክህደት መግለጫ፣ የጦርነት መቀስቀሻ፣ የበሬ ወለደ የሃሰት ወሬ ማራገቢያ መድረክ ማድረጋቸው የፌስ ቡክ ጀግኖችና አርበኞች የላቀ የሥራ ውጤት ነው፡፡

በማህበራዊ ሚዲያ የሚካሄድ የሃሳብ ፍጭት የጦርነት አውድማና የተደበቁ ዕኩይ ማንነቶች የሚገለፁባቸው ሳይሆኑ መንግሥትን በአግባቡ የሚተቹ፣ ግድፈቱን የሚያርሙና የማስተካከያ መንገድ የሚያመላክቱ፣ ያላስተዋለውን የሚጠቁሙ መሣሪያዎች ሊሆኑ ሲገባ ፤ እነርሱ የፈሩትን ተግባር ሌላው ምንም የማያውቀውና በስሜት የሚነዳው ሰው እንዲፈፅምላቸው ተንበርክከው የሚለምኑበት መድረክ አድርገውታል፡፡

ከሌሎች አገሮች ልምድ መረዳት የሚቻለው መንግሥታት ወይም ተቋማት በማኅበራዊ ሚዲያ ለሚደርስባቸው ወቀሳ የአፀፋ አስተያየቶችን የሚጽፉ ሠራተኞችን እንደሚቀጥሩና የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳዳቢዎች አደረጃጀት እንደሚፈጥሩ ሁሉ በእኛ አገርም የመንግሥትን ተግባር አወድሰው፣ ልማታዊ ሥራውን አጉልተው ሲገልፁ በተደራጁ የፌስ ቡክ ተሳዳቢ ሰዎች ተሸማቅቀው ዝም እንዲሉ የተጠናከረ የተሳዳቢዎች ኮሚቴ እንደተዋቀረ በጉልህ ይታያል፡፡

ለምሳሌ የቻይናው መሪ ሁጂንታኦ የቻይናን መልካም ገጽታ ለመገንባት ጥራት ያላቸው የድረ-ገፅ አስተያየት ሰጪ ጓዶች መኖር እንዳለባቸው በመግለፃቸው የቻይናው የባህል ሚኒስትር 300,000 የሚሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያ አስተያየት ሰጪ “ኮሜንት” አድራጊዎችን በቋሚነት በማሰልጠንና በማሠማራት በቻይና የባህል ሚኒስትር_ ሥር እየሠሩ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ በቁጥር በእጅጉ የላቁት ግን “ባለጌ፣ ከሃዲ፣ አሽከር፣ ተላላኪ፣ ሰላይ” ወዘተ...የሚሉ የተለመዱና እጅግም የባሱ ጋጠወጥነት የሚንፀባረቅባቸውን ስድቦችን በመሳደብ ማኅበራዊ ሚዲያውን እያቆሸሹትና ለኅብረተሰብ በጎ ለውጥ የሚውለውን ታላቅ መሣሪያ አገር ለማፍረስ ተግባር እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

ዛሬ በኢትዮጵያ ብዙ ለውጥ አለ፤ ኅብረተሰቡ ማንኛውንም ክንውን የሚያውቀው ፌስ ቡክ ላይ በሚለጠፍለት የሃሰትና የተጋነነ አሉባልታ ሳይሆን እራሱ በዓይኑ ከሚያየውና ከሚረዳው ገሀድ እውነታ ነው፡፡ በርግጥ አንዳንዶች የአገር ፍቅር ያላቸው፣ የመንግሥትን ጥረት የሚገነዘቡ፣ ካሳለፉት መራራ ታሪክ ዛሬ ያገኙት ሰላምና እድገት ቀጣይነቱ የሚረጋገጠው በሰላማዊ መንገድ ብቻ መሆኑን የሚረዱ፣ የሚፅፉትና የሚያስተላልፉት መረጃ የማይናቅና ገንቢ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይህንን በጎ ግንዛቤ እየፈጠረ ያለውን ሥራቸውንም ወደፊት በእውነት ላይ በተመሰረተ መረጃ ማድረሳቸውን ይቀጥላሉ፡፡

ሰሞኑን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ እየተናፈሱና እየተሰራጩ ያሉ የሃሰት ወሬዎችም የእነዚሁ የፌስ ቡክ አሉባልተኞች ተግባር ናቸው፡፡ ግንባታ ቆመ፣ ሠራተኞች ተባረሩ፣ የሥራ መሣሪያዎች ወደ መሀል አገር እየተጫኑ ነው ወዘተ... ተራ ወሬዎች አሰራጮቹን ከግምት ላይ የሚጥልና ወራዳነት የተላበሰ ተግባር ነው፡፡

የዛሬ ስድስት ዓመት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለትና ሥራውን ለፍጻሜ ለማብቃት በሦስት ፈረቃ ለ24 ሰዓት ርብርብ ላይ የሚገኘው ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ የመላ አገሪቱ ሕዝቦች ተስፋ፣ የዜግነት አሻራቸው ያረፈበት፣ የአገሪቱን የወደፊት እድገት የሚያረጋገጥ፣ ለበርካታ ዜጎች የሥራ መስክ የፈጠረ፣ መላው ኅብረተሰብ በተስፋ የሚጠብቀው ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ዕድገት እንደ ውስጥ እግር እሳት የሚያንገበግባቸው ጠላቶቿ እና የራሷ ባንዳና ከሃዲ ልጆቿ በግድቡ ላይ በተለያዩ መንገዶች ሲያሟርቱበት እነሆ ሥራው በስኬት እየተገባደደ እነርሱም የመጨረሻ መፍጨርጨራቸውን ቀጥለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የቱንም ያህል የአሉባልታና የሃሰት ወሬዎች ቢናፈሱ መላ የአገሪቱ ሕዝቦችን ያስተሳሰረ፣ ለአንድ ዓላማ ያሰለፈና አገራዊ መግባባትን በተግባር ያሳየ ታላቅ ግድብ ሥራ ለአፍታ እንኳ እንደማይቆም ማንም ልብ ሊል የሚገባው ነው፡፡ በሃሰት የፌስ ቡክ የወሬ ግርግር እውነት እውነትነቱን አይለውጥም!

 

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ

 

ኤች. አይ. . /ኤድስን ለመከላከል በተደረጉ ጥረቶች የመጡ ለውጦችን ተከትሎ ያለው መዘናጋት በዚሁ ከቀጠለ የቫይረሱ ሥርጭት ዳግም በማንሠራራት ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል የፌዴራል ኤች. አይ. ./ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ገለፀ፡፡

ጽህፈት ቤቱ ኤች. አይ. ./ ኤድስን መከላከልና መቆጣጠርን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት ባካሄደው የምክክር መድረክ ላይ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከበደ ወርቁ ከአስር ዓመታት በፊት የቫይረሱን ሁለንተናዊ ተፅዕኖ በመቀነስና በመከላከል ረገድ ትልቅ ስኬት ቢመዘገብም ቀደም ሲል የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የተፈጠረው መዘናጋትና ትምህርታዊ እንቅስቃሴዎች መዳከም በዚሁ ከቀጠለ ቫይረሱ ዳግም በማንሠራራት ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ፤ ቫይረሱን ለመከላከል በአመራሩ፣ በባለድርሻ አካላት፣ በችግሩ ባለቤቶችና በህዝቡ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እየተቀዛቀዙ መምጣታቸውና በበሽታው ምክንያት የሚከሰተው ሞት በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ፣ እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ጉዳዩን የመደበኛ ሥራቸው አካል አለማድረጋቸው ለቫይረሱ ሥርጭት ማንሠራራት ምክንያት ሆኗል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ሁሉም አካላት ኤች. አይ. ./ ኤድስን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራን በኃላፊነት በመያዝ በጉዳዩ ዙሪያ እንዲወያይና እንዲመክር በማድረግ ከዚህ በፊት የተገኘውን ውጤት ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የቫይረሱ ሥርጭት በአገር አቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 2 በመቶ ሲሆን፤ ይህም አገሪቷ በቫይረሱ ወረርሽኝ ውስጥ መሆኗን የሚያሳይ እንደሆነ ከፌዴራል የኤች. አይ. ./ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

አስናቀ ፀጋዬ

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።