Items filtered by date: Saturday, 07 October 2017

 

የውድድር ዓመቱ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከመጀመራቸው ቀደም ብሎ ክለቦች ራሳቸውን ለማዘጋጀት በያሉበት አካባቢ በተለያዩ ስያሜዎች የተዘጋጁ ጨዋታዎች ላይ ይካፈላሉ። በዚህ መሰረት በርካታ ክለቦችን በፕሪሚየር ሊጉ የሚያ

ሳትፈው ደቡብ ክልል «የደቡብ ሲቲ ካፕ ዋንጫ» በሚል በክልሉ የሚገኙ ክለቦችንና ተጋባዦችን በማሳተፍ ያደረገው ውድድር ባለፈው ሳምንት በአርባ ምንጭ ከተማ አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል። በተመሳሳይ በፕሪሚየር ሊጉ የሚካፈሉ በርካታ ክለቦች የሚገኙበት አዲስ አበባም «የአዲስ አበባ ዋንጫ» በሚል ስያሜ ውድድሩን ለማድረግ ከቀናት በፊት የምድብ ድልድል ይፋ አድርጓል።

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለአስራ ሁለተኛ ጊዜ ያሰናዳው ይህ ውድድር በስምንት ክለቦች መካከል ከነገ ጀምሮ በሚካሄዱ ጨዋታዎች የሚከናወን ይሆናል። ውድድሩ ከዚህ ቀደም ከመስከረም 20 እስከ ጥቅምት 4 ድረስ ይከናወናል ተብሎ መርሀ ግብር ቢወጣለትም በዝናብ ምክንያት የአዲስ አበባ ስታዲየም ለጨዋታ ምቹ አይሆንም በሚል ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 12 ድረስ ለማድረግ ፌደሬሽኑ እንደወሰነ አስታውቋል።

በውድድሩ አዲስ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ያደጉ ክለቦችን ለማሳተፍ ፌዴሬሽኑ ፍላጎት የነበረው ሲሆን በሌሎች ጨዋታዎች ምክንያት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ እንደቀረ ታውቋል። እንደ ሶከር ኢትዮጵያ ዘገባ የዕጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓቱ ከመከናወኑ በፊት ፌደሬሽኑ ለክለብ ተወካዮች የውድድሩን ደንብ በተመለከተ ገለፃ ያደረገ ሲሆን ሊሻሻሉ የሚገባቸው የውድድር ደንቦች ላይ ውይይት ተደርጓል። ውድድሩን የሚያሸንፉ ተጋባዥ ክለቦችን በተመለከተ የሽልማቱ ጉዳይ ላይ የደንብ መሻሻያ መደረጉ የተገለፀ ሲሆን ተጋባዥ የክልል ክለቦች ውድድሩን በአሸናፊነት የሚያጠናቅቁ ከሆነ ዋንጫ መውሰድ አለባቸው የሚል ጥያቄ ከክለቦች በመነሳቱ በድምፅ ብልጫ ፌዴሬሽኑ ጥያቄውን ተቀብሎታል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የምድብ አባት ሆነው የዕጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓቱ የተከናወነ ሲሆን የሁለቱ ክለቦች የምድብ አባትነት ከደጋፊ ብዛት አንጻር የተሻለ የሜዳ ገቢ ለማግኘት እንደሆነ ታውቋል። በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ቡና የፕሪሚየር ሊጉ እንግዳ ክለብ የሆነውና በዚህ ውድድር በተጋባዥነት ከሚሳተፈው ጅማ አባ ጅፋር ጋር ነገ አስር ሰዓት ላይ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል። በተመሳሳይ ደደቢት የፕሪሚየር ሊጉ ተሰናባች ክለብ የሆነውን አዲስ አበባ ከተማን ስምንት ሰዓት ላይ የሚገጥም ይሆናል።

ጨዋታዎቹ የፊታችን ማክሰኞ ቀጥለው ሲውሉም ተጋባዥ ሆኖ የመጣው አዳማ ከተማ ኤሌክትሪክን የሚገጥም ይሆናል። የፕሪሚየር ሊጉ ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመከላከያ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታም በዕለቱ የሚጠበቅ ይሆናል።

ሁሉም ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚከናወኑ ይሆናል። በዚህም መሰረት ይፋ በተደረገው የስታዲየም የመግቢያ ዋጋም ትሪቡን 150 ብር፣ ግራ እና ቀኝ ጥላ ፎቅ 100 ብር፣ ከማን አንሼ ወንበር ያለው 50 ብር፣ ከማን አንሼ ያለ ወንበር እና ካታንጋ 20 ብር፣ ሚስማር ተራ እና ዳፍ ትራክ 10 ብር እንደሆነ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

 

ቦጋለ አበበ

 

 

Published in ስፖርት

በአፍሪካ አገራት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ጋና ከኡጋንዳ ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል ፤

 

2018 የሩሲያ የዓለም ዋንጫ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ከትናንት ጀምሮ በርካታ የዓለማችን አገራት በማጣሪያ ጨዋታዎች ተጠምደዋል። በዓለም ዋንጫው የአምስት አገራት ኮታ ያላት አፍሪካም በተለያዩ አምስት ምድቦች አንደኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ አገራትን ወደ ዓለም ዋንጫው ለመሸኘት ከትናንትን ጀምሮ እስከ ነገ ድረስ ጨዋታዎችን ታስተናግዳለች። የእነዚህን ጨዋታዎች ውጤት ሳይጨምር የትኛው የአፍሪካ አገር ወደ ሩሲያው የዓለም ዋንጫ የማለፍ እድል ይኖረዋል የሚለውን በየምድቡ እንደሚከተ ለው ይተነተናል።

ምድብ 1

በምድብ አንድ ከተደለደሉት አራት አገራት መካከል ጊኒና ሊቢያ በቀጣዮቹ ማጣሪያዎች ውጤታቸው ምንም ይሁን ምን ወደ ዓለም ዋንጫው እንደማያቀኑ ቀድመው አረጋግ ጠዋል። ይህም በምድቡ ቱኒዚያና ዲሞክራቲክ ኮንጎ ብቻ ተስፋ ይዘው እንዲጓዙ አድርጓቸ ዋል። ቱኒዚያ አስር ነጥብ በመያዝ ዲሞክራቲክ ኮንጎን በሦስት ነጥብ ርቃ ምድቡን ትመራለች። ይህም ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር በቀጥታ ወደ ዓለም ዋንጫው ለማቅናት አራት ነጥብ ብቻ በቂዋ ነው። ዲሞክራቲክ ኮንጎ በአንጻሩ ከቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታ ስድስት ነጥብ መሰብሰብ ብቻም ሳይሆን የቱኒዚያን መሸነፍ ትጠብቃለች። ይሁን እንጂ ቱኒዚያ በምድቡ ቀደም ብለው መውደቃቸውን ካረጋገጡት አገራት ጋር በሚኖሯት ሁለት ጨዋታዎች ትሸነፋለች ተብሎ ስለማይጠበቅ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ወደ ዓለም ዋንጫው የማቅናት እድሏ ጠባብ ይሆናል። በዚህም መሰረት ዛሬ ጊኒ ቱኒዚያን ስትገጥም ዲሞክራቲክ ኮንጎ ከሊቢያ ጨዋታዋን ታደርጋለች።

ምድብ 2

የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ካሜሩንና በአፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ ደረጃ ያላት አልጄሪያ በዚህ ምድብ ቀድመው ወደ ዓለም ዋንጫ እንደማያልፉ ያረጋገጡ አገራት ሆነዋል። በአፍሪካ ዋንጫ ላይ መሳተፍ ያልቻለችው ናይጄሪያ በአንፃሩ በዚህ ምድብ ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የተሻለ እድል አላት። ናይጄሪያ ምድቡን በአስር ነጥብ በቀዳሚነት እየመራች በሦስት ነጥብ ዝቅ ብላ ሁለተኛ ላይ የምትገኘው ዛምቢያን ዛሬ ትገጥማለች። የዛሬውን ጨምሮ በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ናይጄሪያ ሁለት ነጥብ ብቻ ማግኘት ከቻለች የሩሲያን ትኬት መቁረጥ ትችላለች። ዛምቢያ ሁለቱን ጨዋታዎች ማሸነፍ ከቻለች የዓለም ዋንጫ ተስፋዋ ላይ ነፍስ መዝራት ብትችልም በግብ ልዩነት ቀዳሚ ሆና ወደ ሩሲያ ለማቅናት ቢያንስ በሦስት የግብ ልዩነት ናይጄሪያን ማሸነፍ ይኖርባታል።

ምድብ 3

በዚህ ምድብ የሚገኙ አራቱም አገራት ወደ ዓለም ዋንጫው የማለፍ ተስፋቸው አላከተመለትም። ኮትዲቯር ምድቡን በሰባት ነጥብ በቀዳሚነት ስትመራ ሞሮኮ በስድስት፤ጋቦን በአምስት፤ ማሊ በሁለት ነጥብ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘው ይከተላሉ። ኮትዲቯር በሁለቱ ጨዋታዎች አራት ነጥብ መሰብሰብ ከቻለች ያላት የግብ ልዩነት ተደምሮ የማለፍ እድሏ የተሻለ ይሆናል። በዚህ ምድብ እያንዳንዱ ጨዋታ በአራቱም አገራት የዓለም ዋንጫ ተስፋ ላይ ልዩነት የሚፈጥር ይሆናል። በዚህም መሰረት ትናንት ምሽት ኮትዲቯር አራተኛ ላይ የምትገኘው ማሊን ስትገጥም ዛሬ ሞሮኮ ጋቦንን ታስተናግዳለች።

ምድብ 4

ፊፋ የደቡብ አፍሪካና ሴኔጋል ጨዋታ እንዲደገም ማድረጉን ተከትሎ በዚህ ምድብ የትኛው አገር ወደ ዓለም ዋንጫ ያልፋል የሚለውን መገመት አዳጋች ነው። ቡርኪናፋሶና ኬፕቨርዴ በስድስት ነጥብ አራት ጨዋታ አድርገው ምድቡን ይመራሉ። ሴኔጋል በሦስት ጨዋታዎች አምስት፤ ደቡብ አፍሪካ በሦስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ይዘው ይከተላሉ። ቡርኪናፋሶ በግብ ልዩነት በልጣ ምድቡን በቀዳሚነት ብትመራም ቀሪዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ ወደ ዓለም ዋንጫው ለማቅናቷ መተማመኛ አይሆንም። ምክንያቱም በአንድ ነጥብ ዝቅ ብላ የምትገኘው ሴኔጋል ቀጣይ ሦስት ጨዋታዎች የሚቀሯት እን እደመሆኑ መጠን በነዚህ ጨዋታዎች ሙሉ ዘጠኝ ነጥብ መሰብሰብ ከቻለች ቡርኪናፋሶን ልትገለብጥ ትችላለች። ኬፕቨርዴም ቀሪዎቹን ጨዋታዎች በማሸነፍና የሌሎቹን መሸነፍ መሰረት አድርጋ የማለፍ እድል ይኖራታል። አንድ ነጥብ ያላት ደቡብ አፍሪካም ብትሆን በሂሳባዊ ስሌት ሦስቱን ጨዋታዎች አሸንፋ የሌሎ ቹን ውጤት ጠባቂ ብትሆ ንም የማለፍ እድሏ አልተዳፈነም። የዚህ ምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉም ደቡብ አፍሪካ ቡርኪናፋሶን፤ ሴኔጋል ኬፕቨርዴን የምትገጥም ይሆናል።

ምድብ 5

በዚህ ምድብ ኮንጎ በአንድ ነጥብ ተስፋዋ የተሟጠጠ አገር ናት። በዘጠኝ ነጥብ ምድቡን የምትመራው ግብፅም ብትሆን በቅርብ ርቀት የሚከተሏትን አገራት ጥላ ለማለፍ ቀሪዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ ግዴታዋ ነው። በሰባት ነጥብ የምትከተለው ኡጋንዳ ዛሬ ጋናን ማሸነፍ ካልቻለችና ግብፅ ኮንጎን በነገው ጨዋታ ከረታች ለፈርኦኖቹ የዓለም ዋንጫው መንገዱ ጨርቅ ይሆንላቸዋል። በአምስት ነጥብ ሦስተኛ ላይ የሚገኙት ጥቁር ከዋክብት ቀሪዎቹን ጨዋታዎች ማሸነፍ ብቻም ሳይሆን የግብፅና ኡጋንዳ መሸነፍ የዓለም ዋንጫ ተስፋቸውን ያለመል መዋል።

 

ቦጋለ አበበ

Published in ስፖርት

ከዓመት በፊት የተሻሻለው የአምስተርዳም ማራቶን ክብረወሰን ዘንድሮ በተስፋዬ አበራ ሊሰበር ይችላል

 

በዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ ያለው የአምስተርዳም ማራቶን ከሳምንት በኋላ ሲካሄድ የውድድሩ አዘጋጆች የቦታው ክብረወሰን እንደሚሻሻል እምነት አሳድረዋል። በሆላንዷ መዲና በሚካሄደው በዚህ ውድድር ክብረወሰኑን ያሻሽላሉ ተብለው ከሚጠበቁት አትሌቶች መካከልም ኢትዮጵያዊው ተስፋዬ አበራ ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል።

ባለፈው ዓመት የዱባይ ማራቶን 20424 በሆነ ሰዓት ሲያሸንፍ የራሱን ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ የቻለው ተስፋዬ አበራ በተደጋጋሚ በታላላቅ የማራቶን ውድድሮች ላይ አሸናፊ መሆኑ የአምስተርዳም ማራቶን ክብረወሰን የሆነውን 20521 ሰዓት እንዲያሻሽል ዕጩ አድርጎታል። የሃያ አምስት ዓመቱ ተስፋዬ አበራ በማራቶን ከዓለም አስራ ሦስተኛውን ፈጣን ሰዓት የያዘ አትሌት ሲሆን በዱባይ ካሸነፈ በኋላ በሐምቡርግ ማራቶን ሌላ ድል አስመዝግቦ በውድድር ዓመቱ ስኬታማ ጊዜ ማሳለፍ ችሏል።

አምስተርዳም ማራቶን የመጨረሻው እንደሚሆን የተነገረለት ኬንያዊው አሞስ ኪፕሩቶ ከተስፋዬ አበራ በመቀጠል በውድድሩ ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት የያዘ አትሌት ሆኗል። ይህ አትሌት በደቡብ ኮሪያ ሴዑል ማራቶን ባለፈው ዓመት አሸናፊ ሲሆን ያስመዘገበው 2:05:54 ቀድሞ ከነበረው የራሱ ምርጥ ሰዓት ከሁለት ደቂቃ በላይ የተሻለ ነበር። ይህም አምስተርዳም ላይ ተስፋዬ አበራን በእጅጉ ይፎካከረዋል ተብሎ እንዲጠበቅ አድርጓል።

በተመሳሳይ ሌላኛው ኬንያዊ ኤድዊን ኪፕቶ ባለፈው ዓመት በዚሁ በአምስተርዳም ግማሽ ማራቶን ውድድር ባሳየው ድንቅ ብቃት መሰረት ዘንድሮ ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በግማሽ ማራቶን 59 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ የሆነ የራሱ ምርጥ ሰዓት ያለው ኪፕቶ በማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ ተወዳዳሪ ቢሆንም ለአምስተርዳም ጎዳናዎች እንግዳ አለመሆኑ ከጠንካራ ተፎካካሪዎች ተርታ አሰልፎታል።

ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶች ባለፉት አስራ ሰባት ዓመታት በአምስተርዳም ማራቶን ከሌሎች አገራት አትሌቶች በተሻለ በርካታ ጊዜ አሸንፈዋል፤ የውድድሩን ክብረወሰንም ደጋግመው መሰባበር ችለዋል። ይህ የበላይነታቸውም ውድድሩ ዘንድሮ ለአርባ ሁለተኛ ጊዜ ሲካሄድ እንደሚቀጥል ይታመናል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለይም በሴቶች ባለፉት አስራ ሰባት ውድድሮች አስር ጊዜ ማሸነፍ ሲችሉ ኬንያውያን ቀሪዎቹን አሸንፈዋል። ኢትዮጵያውያን በእነዚህ አስር ድሎቻቸው በሦስቱ የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር ሲያሸንፉ ኬንያውያን ከሰባቱ ድሎቻቸው በአንዱ እንኳን የቦታውን ክብረወሰን ማሻሻል አልቻሉም። ይሁን እንጂ በወንዶች ኬንያውያን አትሌቶች ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች አኳያ የተሻለ ታሪክ አላቸው። ኬንያውያን አምስተርዳም ላይ አስራ ሰባት ጊዜ በማሸነፍ ትልቅ የበላይነት አላቸው። ኢትዮጵያውያን ደግሞ አምስት ጊዜ ብቻ በዚህ ድል ደምቀዋል። ኬንያውያን ከእነዚህ ድሎቻቸው ዘጠኝ ያህሉን ማሸነፍ የቻሉት የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል ሲሆን ኢትዮጵያውያን ከአምስት ድሎቻቸው ሁለቱን የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል ነበር ማሸነፍ የቻሉት።

በአምስተርዳም ማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ ማሸነፍ የቻለችው ኢትዮጵያዊት አትሌት እ..1997 ላይ እልፍነሽ አለሙ ስትሆን በውድድሩ ያስመዘገበችው ሰዓትም 23737 ነበር። 2000 ላይ አትሌት አበባ ቶላ 22954 በሆነ ሰዓት ሁለተኛዋ አሸናፊ ነች። በቀጣዮቹ ሁለት ውድድሮችም 2001እና 2002 ላይ ሽታዬ ገመቹ 22840 በሆነ ሰዓት ስታሸንፍ ጌጤ ዋሚ 22219 በሆነ የውድድሩ ክብረወሰን አሸናፊ ሆናለች። 2005 ላይ ቁጥሬ ዱለቻ 23003 በሆነ ሰዓት ስታሸንፍ 2009 ላይ እየሩሳሌም ኩማ 22743 በሆነ ሰዓት ባለ ድል ሆናለች። 2011 ላይ በዚህ ውድድር 22208 በሆነ የውድድሩ ክብረወሰን ማሸነፍ የቻለችው የኦሊምፒክ ቻምፒዮኗ ቲኪ ገላናም በርቀቱ የስኬት ጉዞ የጀመረችው በዚህ ውድድር ነበር። ይህ ክብረወሰን ግን ከዓመት በላይ ሳይቆይ በቀጣዩ ዓመት ውድድር በመሰረት ሀይሉ 22109 በሆነ ሰዓት ተሻሽሎ እስካሁንም የቦታው ክብረወሰን ሆኖ ዘልቋል። ከዚህ በኋላ 2014 ላይ 22835 በሆነ ሰዓት ማሸነፍ የቻለችው ቤተልሄም ሞገስና ባለፈው ዓመት 22321በሆነ ሰዓት ማሸነፍ የቻለችው መሰለች መልካሙ ለድል ቢበቁም የቦታውን ክብረወሰን ማሻሻል አልቻሉም።

በወንዶች በጣት የሚቆጠሩ ድሎችን በአምስተርዳም ማራቶን ካጣጣሙ ኢትዮጵ ያውያን አትሌቶች መካከል የረጅም ርቀት ንጉሱ ኃይሌ ገብረስላሴ አንዱ ነው። ኃይሌ እ..2005 ላይ ውድድሩን 20620 በሆነ ሰዓት ሲያሸንፍ የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር ነበር። ከአምስት ዓመት በኋላም ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ጌቱ ፈለቀ 20544 በሆነ ሰዓት የቦታውን ክብረወሰን አሻሽሎ ማሸነፍ ችሏል። አሁን ላይ የቦታውን ክብረወሰን 20521 በሆነ ሰዓት ባለፈው ዓመት ያስመዘገበው ኬንያዊው ዳንኤል ዋንጂሩ ነው። ኃይሌና ጌቱ የውድድሩን ክብረወሰን በማሻሻል የሚታወሱ አትሌቶች ቢሆኑም ለመጀመሪያ ጊዜ ለድል የበቃው ዘሪሁን ግዛው 21152 በሆነ ሰዓት እ..1990 ላይ ነበር። ከዓመት በኋላም ተስፋዬ ጣፋ 21326 በሆነ ሰዓት ማሸነፍ ችሏል። 1994 ላይ ደግሞ ተስፋዬ ኢቲቻ 21556 በሆነ ሰዓት በማሸነፍ በውድድሩ ይታወሳሉ።

 

ቦጋለ አበበ

 

 

 

Published in ስፖርት
Saturday, 07 October 2017 20:48

«የማይመስል ነገር...»

 

ሰዎች አጉል ሰዓት አጉል ነገር ላይ ሲገኙ የመጀመሪያ አማራጫቸውን መዋሸት ነው የሚያደርጉት። እልም ያለ ነጭ ውሸት ይዋሻሉ፤ ያልሆነውን ሆነ ይላሉ፤ የሆነውን አልሆነም ይላሉ፤ በጭራሽ ሊሆን እንደማይችል የሚታወቀውን ደግሞ በእርግጠኝነት ይተርኩታል።

አንድ ሰው መዋሸቱ አንድ ጥፋት ሆኖ ሳለ የዋሸውን ሰው እንዳይጠራጠርም እንዳያምንም አድርጎ ግራ ሲያጋባው ማየት ደግሞ ያስቸግራል። «ከዋሹ አይቀር ደኅና ውሸት መዋሸት ነውያሰኛል። ልንገራችሁ፥ መንገድ ላይ ነው፤ ከአንዱ የእግረኛ መንገድ ወደሌላው ለመሻገር ከተሰበሰብን ሰዎች መካከል ነው ያየሁት። ከሁሉም ሰው የቸኮለው የሚመስል አንድ ወጣት ነው።

ታዲያ ስልክ ይዞ እያነጋገረ ነው፤ «ሄሎ...አዎን እየመጣሁ ነው! ያው ታክሲ ውስጥ ነኝ» አላለም?! አጋጣሚ መንገዱ ግራና ቀኝ ሆነው ስርዓት የሚያሲዙት ልጆች መኪናዎቹን አስቁመው እግረኛው እንዲያልፍ ፈቀዱ። ልጁም ወደታክሲ ተራው በፍጥነት አመራ። እንደው አልደረስኩና አልጠየኩትም እንጂ አሁን እንዲህ ያለን ውሸት ምን ይሉታል? በዛኛው አቅጣጫ የተዋሸው ሰው ምን ያስብ ይሆን የሚለው አያሳስብም?

በእርግጥ መዋሸት የማይችሉ ሰዎች ናቸው የማይሆን ውሸት የሚናገሩት ይባላል። ወይም ደግሞ በጣም ደፋር መሆን አለባቸው። መቼም የእኛ ሰው ሰውን ሲዋሽ፤ በብዛት ለክፋት ሳይሆን ይሉኝታ እየያዘው ነው። «ወደቅሁ ብል ሰው ምን ይለኛልብለው ፈተና ማለፋቸውን የሚናገሩ ተማሪዎች አሉ። ከዛ የጀመረ ይሉኝታን ፍራቻ የወለደው ውሸት አድጎ ዝሆን ያክልና አገር ላይ ያርፋል!

መቼ ደግሞ አንድ ቀልድ ሲወራ ነበር፥ ቀልድ ይሁን እውነት ግን አልተለየም። ያው ቀልድም ቢሆን አንዳች መነሻ እውነት አያጣም አይደለ? እንዲህ ነው፥ አንዱን ሹፌር ትራፊክ ያስቆመዋል፥ መጠጥ ጠጥቶ እንደሆነ ለማረጋገጥም መመርመሪያ መሣሪያውን ወደሹፌሩ ይልከዋል። ታዲያ መሣሪያው አሽከርካሪው ደኅና አድርጎ የጠጣ ስለመሆኑ ምስክርነት ይሰጣል።

ትራፊኩ ይህን አስተውሎ፥ «መንጃ ፈቃድዎን ይስጡኝ፤ ብዙ ጠጥተዋል? ትንፋሽዎ የሚያሳየው ብዙ መጠጣትዎን ነው። ጠጥቶ ማሽከርከር ወንጀል መሆኑን አያውቁምትራፊኩ ተቆጣ። ይሄኔ አሽከርካሪው ምን ቢል ጥሩ ነው፥ «እኔ ውሃ ነበር የጠጣሁት፤ ፈጣሪ በኪነጥበቡ ወይን አድርጎት ካልሆነ በቀር

አሶሽዬትድ ፕሬስ በያሁ ገጽ ላይ ያስነበበው ዜና ደግሞ እንዲሁ የማይመስል ነገር ይሉት ነው። በምዕራብ አሜሪካ በምትገኝ ዩሚንግ በምትባል ግዛት ማዕከል በሆነች ካስፐር ከተማ አንድ ወሬ ተሰማ። አንድ ሰውዬ ነው አሉ፥ በፊታችን ከሚመጣው ከ2048 ነው የመጣሁት አለ። እንግዲህ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነው። ታዲያ ምን ልሠራ መጣሁ አለ መሰላችሁ፥ «በቀጣይ ዓመት ከተማችንን ያልታወቁ ፍጡራን /aliens/ ሊያጠፉት ስለሚመጡ አሁኑኑ ለቅቀን መውጣት አለብን»

ነብይ በሉት በቃ! በእርግጥ ደግሞ ቢሆንስ ማን ያውቃል? ተስፋ የማይቆርጡ ነጮች በ2012 ዓለም ትጠፋለች ብለው ሲያሟርቱ ቆይተው ነበር፤ ነገር ግን በየቀኑ እየጫጨች ብትሄድም ዓለም አሁንም ድረስ አለች። እናሳ! ማንን ደስ ይበለው ብላ ትጥፋ! አሳፈረቻቸው።

ይህም ሰውየው ታዲያ በኖረባት ከተማ ላይ ጨክኖ፤ ለህዝቡ ግን አዝኖ ከከተማዋ እንዲለቁ ሊያስጠነቅቅ መምጣቱን ደጋግሞ ተናገረ። ከዛም አልፎ ከከተማዋ አስተዳዳሪ ጋር መነጋገር እንዳለበት አሳወቀ። ከከተማዋ 270 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መቀመጫውን ያደረገው የከተማዋ አስተዳዳሪ ግን በተባለው ሰዓት አልተገኘለትም። «ለምን? ለከተማዋ አያስብም ማለት ነው?...» ወዘተ ብላችሁ ለመጠየቅ አትቸኩሉ!

ይህ ሰው ይህን ሁሉ ነገር የሚናገረው መንገድ ላይ እየጮኸ ወይም መድረክ ላይ ሆኖ አይደለም፤ ፖሊሶች ፊት ሆኖ ነው። ፖሊሶችም ያገኙት ይኸንኑ ትንቢት ሲናገር አይደለም፤ ጠጥቶ አካባቢን ሲረብሽ ይዘውት ነው። ስለመጠጣቱ በተመለከተ ለፖሊሶቹ ሲናገር ታዲያ «ኧረ እኔ አልጠጣሁም፤ የላኩኝ ፍጡራን ሰውነቴን በአልኮል ሞልተውት መሆን አለበት። ጊዜን አቋርጪ ከ2048 ወደ 2017 ስመጣም በስህተት ነው። በ2018 ነበር መምጣት የነበረብኝ» ብሎ እርፍ!

ይሄ ሰው ሆድ ያባውን ሆኖበት እነዛ ፍጡራን አትናገር ያሉትን ተናግሮ ካልሆነ በቀር፤ ማን ይሰማዋል! ግን ከምሩ ይሆን እንዴ? ፖሊሶቹ ግን «የማይመስል ነገር...ለማንም አትንገር» ብለው ነው መሰል አለቀቁትም።

 

ሊድያ ተስፋዬ

Published in መዝናኛ
Saturday, 07 October 2017 20:47

ህጉን ወይስ አስከባሪውን?

ወጋ ወጋ በነገር

ህግ አስከባሪ። ጥያቄ አንድ፥ ህግ አስከባሪ ምን ማለት ነው? መልስ አንድ፥ ህግን የሚያስከብር።

ጥያቄ ሁለት፥ ህግ ካለ ለምን አስከባሪ አስፈለገ? ሰውን የሚያህል ማሰብ የሚችልና በምድር ላይ አለ የሚባል ብቸኛው ባለ-አእምሮ ለምን ብሎ ነው ራሱ ያለተቆጪ ህግ የማያከብረው? ስለምን ህግ አስከባሪ ያስፈልገዋል? መልስ ሁለት፥ ምን አውቃለሁ!

ኑሯችን ራሱ ጉዞ ነውና ትዝብታችን ከመንገድ ብዙም አይርቅም፤ ዛሬም መንገድ ላይ ተገኝተናል። መንገድ ላይ በልመና ሥራ ከሚተዳደሩ፣ ድብብቆሽ ይዘው ዕቃ ከሚ ሸጡ፣ ጫማ ከሚያጸዱ፣ጀበሎ (ሱቅ በደረቴ) ይዘው ከሚንቀሳቀሱና መሰል ሥራ ላይ ካሉ ሰዎች በተጨማሪ የመንግስት ሠራተኞች የሆኑ ህግና ደንብ አስከባሪዎች አሉ።

እዚህ ላይ ህግ ያስከብራሉ ወይስ ራሳቸው ይከበራሉ? የሚል ሶስተኛ ጥያቄ ቢመጣ ምላሹ ወደው ባይሆንም ብዙ ጊዜ ህግን ከማስከበራቸው በላይ የሚከበሩት እነርሱ ናቸው የሚል ይሆናል ባይ ነኝ። እና እንዳልኳችሁ መንገድ ላይ አይደለን? መንገዳችን ላይ እንደ ልጅነት «እናገርብሃለሁ» የምንባባልበት ጉዳይ ይገጥመናል። በተለይ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ መኪናዎቻችን/ ታክሲዎቻችን ወይም ተሽከርካሪዎቻችን አካባቢ።

ውይ! ትራንስፖርት? ያላማረረው ካለ አገሩን ጠይቁልኝ። ተሳፋሪም ሁኑ ባለመኪና፥ ጠዋት ከቤት መውጣትና ምሽት ወደ ቤት መግባት እንዲሁ ሲያስቡት ራሱ አሰልቺ ሆኗል። ሞት ሁሉን እኩል እንደሚያደርግ፥ የመንገዱ ነገርም ታክሲ ተጠቃሚውን በእግር ባለመኪናውን ከነመኪናው እኩል ያሰልፈዋል። እንደውም እግረኛ መሆን ሳያዋጣ አይቀርም፤ በዛም ግፊያው የዋዛ ባይሆንም፤ ይሻላል።

ታድያ ታክሲ ተራዎች አካባቢ መንገድ ትራንስፖርት የምንላቸውን የመንግስት ሠራተኞች ጨምሮ ህግ፣ ደንብ፣ መመሪያ፣ ስርዓት፣ ተራ ወዘተ አስከባሪዎች ሳይኖሩና ሲኖሩ ልዩነቱ በግልጽ ይታያል። እነዚህ የተባሉ አካላት ካሉ ሰላማዊው የታክሲ ሰልፈኛው ይረጋጋል፤ በትዕግስት ተራውን ይጠብቃል። አሽከርካሪዎች ሊሄዱ ወደተመደቡበት ቦታ ያለማቆራረጥና ያለዋጋ ጭማሬ ይጭናሉ።

አራተኛ ጥያቄ፥ እነዚህ አካላት ከሌሉስ? መልስ አራት፥ እነዛ አካላት ከሌሉ ከአሽከርካሪዎች ጀምሮ ምን የመሰለ ጥፋት በሁሉም ይሠራል። አሽከርካሪዎች ከታክሲያ ቸው አናት ላይ ያለውን የጉዞ መስመር በእኩልነት በማጠፍ አቆራርጠው ይጭናሉ። የተወሰነም የዋጋ ማስተካከያ ወይም ማሻሻያ ሊያደርጉም ይችላሉ/ያደርጋሉም። በስርዓት ተሰልፎ የቆየው ሰው ግርግር መፍጠር ይጀምራል። ለአያ ሌቦ ሁኔታው ይመቻቻል ማለት ነው። «ኧረ እባካችሁ መሄዳችሁ ላይቀር ለምን አትወስዱንም?!» የተወሰነ ሰው ድምጽ ቢያሰማም ጆሮ ግን የለም።

በእርግጥ ኑሯችን ቀዳዳ የበዛበት ሆኖ ሁሉም ራሱን ብቻ ለማውጣት የሚሯሯጥበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። መቼም ለመክሰስም ለመውቀስም ታክሲ ተራው ቀለል ስለሚለን ነው እንጂ፤ እነርሱ ለትንሽ ፍራንካ መንገዱን እንደሚቆራርጡት ሁሉ ሌላውንም ቆርጠው ቀጥለው የእለት እንጀራቸውን የሚበሉ እንዳሉ ግልጽ ነው። ግን እዚህ ላይ ላነሳ የወደድኩት ሰው ከህግ በላይ ህግ አስከባሪን የማክበሩን ነገር ነው።

ጥያቄ አምስት፥ ከህግና ከህግ አስከባሪ ማን ያስፈራል? መልስ አምስት፥ ኧ?

ጥያቄ ስድስት፥ ህግ አስከባሪው እያስከበረ ያለው ማንን ነው? መልስ ስድስት፥ ድምጸ ተአቅቦ በእርግጥ በሌላ በኩል ስታዩት ህግ አስከባሪውም ከህጉ በላይ የሚያስከብረው ራሱን ነው። «ቆይ! እሠራልሃለሁ» የሚል ህግ አስከባሪ ገጥሟችሁ አያውቅም? ከህግ በላይ የሚሠራልንም የሚሠራብንም ሰው፣ ባለስልጣን፣ህግ አስከባሪ የተባለው ሰው ነውኮ! ሙስና እንደ አሸን የፈላው ከህግ በላይ ህግ አስከባሪው ችግር ስላለበት አይደለምን? ሰዉም ከህግ በላይ ህግ አስከባሪውን ስለሚያከብር! መቼም ዞረን ዞረን መድረሻችን ሙስና ሆኗል! እንግዲህ ዘመኑን የምንከባበርበት፤ ህግንም የምናከብርበት ያደርገዋ! ሰላም!

 

ሊድያ ተስፋዬ

Published in መዝናኛ

ወይዘሮ ቤተልሔም ደጉ

 

«ሴትን ልጅ ህግ ምን ያህል ይጠብቃታል? ብልህስ ብትሆን አይሻልም ወይበዚህ ላይ የተለያዩ ሰዎች በተለያየ መንገድ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። በአብዛኛውም ህግ ቢኖርም እንኳ «...ፌጦ መድኃኒት ነው» እንዲሉ ብልሃቷን ግን ትያዝ ይላሉ። ይህን ሃሳብ እንዳለ ይዘን በጉዳዩ ላይ የህግ ባለሙያዎች ምን ይሉ ይሆን ስንል ወደ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር አቅንተን ነበር። በዛም በማኅበሩ የህግ አማካሪ ከሆነችው ወጣት ወይዘሮ ቤተልሔም ደጉ ጋር ተገናኝተን በአንዳንድ ጥያቄዎች ዙሪያ ተነጋግረናል፤ እነሆ።

አዲስ ዘመን፡- ህግ ምንድን ነው?

ወይዘሮ ቤተልሔም፡- ህግ ማለት በአጭሩ፣ ማኅበረሰቡ ተስማምቶ፣ ይገዛኛል ብሎ በመረጠው መተዳደሪያ መሰረት የዛን ማኅበረሰብ የኑሮ ሁኔታ ይዞ የሚወጣ መመሪያ ማለት ነው።

ተፈጥሮአዊ የምንላቸው በማኅበረሰቡ ተቀባይነት ያላቸውና የሌላቸው ድርጊቶች አሉ። ሰዎች የፈጠሯቸው ህጎችም አሉ። ማኅበረሰቡ በሚኖረው የኑሮ ሂደት ውስጥ ችግር በሚፈጠርበት ሰዓት ወይም መደበኛ ባለው የአኗኗር ዘይቤ ላይ የተለየ ባህሪ በሚታይበት ጊዜ ያንን ባህሪ ወደ መደበኛ ለመመለስ የሚደረግበት፤ ቅደም ተከተላዊ ስነ-ስርዓት ያለበት መመሪያ፣ ማስዳደሪያ ነው። ህግ የተለያዩ ጥቅሞች አሉት፣ ያጠፋን ሰው ያርማል፣ ለሌሎች መማሪያ ያደርጋል፣ እንዲሁም ያጠፋው ሰው እንዲመለስ ያግዛል።

አዲስ ዘመን:- ህግ እና ፍትህ ምንና ምን ናቸው?

ወይዘሮ ቤተልሔም:- ህግ ቅደም ተከተላዊ ስነ-ስርዓት ነው። ይህ ማለት መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች አሉ። አንድን ነገር ህገወጥ ነው ለማለት የተቀመጡ መስፈርቶች አሉ። ያንን መስፈርት መሰረት ባደረገ መልኩ ማስረጃ ላይ /በማስረጃ ህግ/ የሚተዳደር ሲሆን፣ ፍትህ ግን እውነትን ብቻ የያዘ፣ ቅደም ተከተላዊ ስነ-ስርዓት የሌለበት ነው። አንዳንድ ነገሮች በህጉ መሰረት የሚጠይቃቸውን ተፈላጊውን ቅደም ተከተል ላያሟሉ ይችላሉ። በዚህም ፍትሃዊ ያልሆነ መፍትሄ ሊሰጣቸው ይችላል።

በአብዛኛው ህግ የሚሠራው ፍትህን ለማስፈን ነው። አንዱ ወደ አንዱ ሊሄድ ይችላል። በዋናነት ልዩነታቸው ግን ህግ አለ ማለት ፍትህ አለ ማለት አይደለም። ህግ ኖሮ ፍትህ ላይኖር ይችላል። ምክንያቱም ህግ በስርዓትና በማስረጃ ስለሚመራ፣ ፍትህ ደግሞ እውነትን ብቻ የያዘ ስለሆነ።

አዲስ ዘመን:- ሴቶችን ለመጠበቅ የወጡ ህጎች አሉ?

ወይዘሮ ቤተልሔም:- ሴቶችን ለመጠበቅ የወጡ በርካታ ህጎች አሉ። የፍትሄብሔር የሆኑ፣ ከወንጀል ውጪ መብቶቻቸውን የሚያስከብሩ ህጎች እንዲሁም ወንጀል በሚፈጸምበት ሰዓት ደግሞ የሚከላከሉላቸው ህጎች ወጥተዋል። እነዚህም በሲቪል፣ በቤተሰብ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ኮድ ላይ ተጠቅሰው ይገኛሉ። በሁሉም ላይ የሴቶችን መብት የሚጠብቁና የሚደነግጉ፣ እንዲሁም መብታቸው ተጥሶ ሲገኝ መፍትሄ መስጠት የሚቻልበትን ዘዴ የያዙ ህጎች አሉ።

አዲስ ዘመን:- ብዙ ጊዜ የአፈጻጸም ችግር አለ ሲባል እንሰማለን፤ በህግ ዙሪያ የአፈጻጸም ችግር የሚባለው የቱ ነው? ምክንያቱስ ምንድን ነው?

ወይዘሮ ቤተልሔም:- የአፈጻጸም ችግር አለ ሲባል እንደወረደ አይደለም። ክፍተቱን የሚፈጥረው የስነስርዓት ደንቡን ያለመከተል ነው። አንድን ጉዳይ የያዘ ዳኛ ምንም እንኳ የደረሰው ጥቃት ቢሰማውና የሆነው ነገር በጣም ውስጡን ቢነካው ጉዳዩ የሚታየው በክርክር ነው፣ በዚህም አሸናፊና ተሸናፊ አለ። ሁሉም አለኝ የሚለውን ያቀርባል። ተከሳሽም ጠበቃ ኖሮት ነው የሚከራከረው፣ አቃቤ ህግም አለኝ በሚለው ማስረጃ ይሄዳል። በመጨረሻም የታሰበው ውጤት ላይመጣ ይችላል፣ ይህ የአፈጻጸም ችግር ላይሆን ይችላል።

የአፈጻጸም ችግር ያለባቸው አካባቢዎች አሉ። አንዱ በግልጽ ያልተቀመጡ ቃላት ጉዳይ ነው። ለምሳሌ «ጾታዊ ትንኮሳ» ተብሎ «ወሲባዊ ትንኮሳ» ብንል፣ በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት እንዲህ ነው ተብሎ አልተቀመጠም። እንደዛ ተብሎ የሚገኝበት አንቀጽ የለም። አንዳንድ ነገሮች ህጉ ላይ በቀጥታ አልተዳሰሱም። የአፈጻጸም ችግሮች ከሚፈጥሩት አንዱ በቀጥታ ያልተዳሰሱ ጉዳዮችም ናቸው። እና ለማስፈጸም ከባድ ይሆናል።

አንዲት ሴት በደረሰባት ጥቃት አካላዊ ብቻ ሳይሆን የስነልቦና ጉዳት ደርሶባት ይሆናል። ነገር ግን ያንን የሚዳስስ ቀጥታ የተቀመጠ ህግ ስለሌለ ጉዳት ደርሶባት እንኳን በሚገባ ማስፈጸም ላይቻል ይችላል። በዛም ላይ ክርክር ነው፣ ሁለም አለኝ የሚለውን ምርጥ የሆነ መከላከያ ነው የሚያቀርበው። እናም እንደተፈለገውና ደረሰ እንደተባለው በደል ይመጥናል የሚባል ቅጣት ላይወሰን ይችላል።

ይሄ በማኅበረሰቡ ግፊት እና በመገናኛ ብዙኅን፣ የህግ አውጪ አካላት ላይ ተጽእኖ ማድረግና በጥቅሉ ግንዛቤ መፍጠር ለዚህ መፍትሄ ይሆናል። ምክንያቱም የህዝቡ የእውቀት ደረጃ በጨመረ መጠን የህግ አውጪውም የእውቀት ደረጃ ይጨምራል። በዚህም ያልታዩ ነገሮች ይዳሰሳሉ፣ ለማስፈጸም ከባድ የሆኑ ነገሮችም ይቀንሳሉ።

ለማስፈጸም ሌላው ከባድ ነገር የቴክኖሎጂ ችግር ነው። ወደማኅበራችን በብዛት ከሚመጡ ጉዳዮች መካከል የአባትነት ጉዳይ ነው። በጓደኝነት ይረገዛል፣ ልጁ ሲወለድ አባት ይክዳል። እናም ያ ሰው «አባት ነው አይደለምየሚለውን ለማረጋገጥ አሁን ባለንበት የዓለም ስልጣኔ በጣም ቀላል ነው፣ ዲ.ኤን.ኤ ምርመራ አለ። እኛ አገር ግን ከባዱ ሂደቱ ነው። የሚጠየቀው ብር ከፍተኛ ነው። እየተከራከሩ ያሉት ያንን ብር ከፍሎ የማስመርመር አቅም ያላቸው ሰዎች አይደሉም። የአፈጻጸም ችግር በዚህም ይመጣል።

ሌላው አንድን ነገር ለመጠየቅ የጊዜ ገደብ አለ። ህግ ከዚህ ጊዜ እስከዚህ ጊዜ ይህን ጥያቄ መጠየቅ ይቻላል ብሎ ያስቀምጣል። በሰዓቱ ወደሚመለከተው አካል አለመሄድም ለማስፈጸም ችግር ምክንያት ይሆናል። በዚህ ላይ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችም በጊዜ ወደ ህግ አስከባሪ አካላት ባለመሄዳቸው ነው። ስለዚህ ህግ አውጪ፣ አስፈጻሚ አካላት የምንላቸው፣ እንደ ሀኪም፣ ፖሊስ እና መሰል ጋር እንዲሁም ተበዳይ ባለጉዳዮች ጋር ክፍተት አለ። ከሁሉም አንጻር ለማስፈጸም ከባድ ይሆናል። ነገር ግን ግንዛቤ ከተፈጠረና የህዝቡ የእውቀት ደረጃ ከፍ ካለ መብትን የመጠየቅ ብሎም የማስከበር ሁኔታ እየጨመረ ይሄዳል።

አዲስ ዘመን:- የአፈጻጸም ክፍተት ባይኖር ኖሮ ህግ ሴቷን ምን ያህል ይጠብቃታል? ፍጹምነትስ አለው?

ወይዘሮ ቤተልሔም:- ህግ ላይ ፍጹምነት በጊዜ ሂደት የሚመጣ ነው። ትላንት ላይ መጥፎ ሥራ ያልነበረ ፣ነገ ላይ ጥፋት ሆኖ ሊገኝ ይችላል። ፍጹም ነው የምንልበት ቦታ ላይ አይደለም ያለነው። እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ በውጪውም ዓለም ላይ ፍጹም የሆነ ህግ አይደለም ያለው፣ በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄድ ነው።

እንደእኔ አመለካከት በህግ ደረጃ በፊት ከነበርንበት አንጻር ብዙ መጥተናል። በፊት እውቅና የማይሰጣቸው የሴቶች መብቶች አሁን እውቅና ተሰጥቷቸው፣ መብት ሆነው ሴቶች እየተለማመዷቸው ይገኛሉ። ነገር ግን የሚጎድሉት ነገሮች የሉም የምንለው ህግ አይደለም። የዛኑ ያህል የሚጎድሉ ነገሮች አሉ።

አዲስ ዘመን:- ታድያ ሴትን ከህግ እና ከብልሃት የቱ ይጠብቃታል?

ወይዘሮ ቤተልሔም:- በእኔ አመለካከት ህግም ብልሃትም ሴቷን ይጠብቋታል። ህግ ጋር ስንሄድ መብት ነው፣ መብት ስንል አጥቂም ተጠቂም መብት አለው። የበደለም የተበደለም፣ ሁለቱም በህግ ዓይን መብት አላቸው። በተለይ በወንጀል ከሆነ ተከሳሹ በደንብ በማያሻማ ሁኔታ ጥፋተኛነቱ መረጋገጥ አለበት፣ ምክንያቱም የዛን ሰው መብት ነው የምንገድበው። የአንዱን መብት ለመጠበቅ የሌላውን መብት ማሳጣት አለ። ህግ ይህን እያማከለ ስለሚሄድ ብልሃት ብዙውን ሚና ይጫወታል ባይ ነኝ። ነገር ግን ህግም አለ፣ ህግም ደግሞ ይጠብቃታል።

ይህ ጉዳይ እንደሁኔታው ይለያያል። ለምሳሌ የቤተሰብን ህግ ብናይ ብልሃት ነው ሴትን የሚጠብቃት አንልም። ንብረትን በተመለከተ ህጉም ይጠብቃታል። ወንጀል ላይ በምንሄድበት ጊዜ ደግሞ ብልሃትም የሚጠብቃት ጊዜ አለ። አንዲት ሴት ተደፍራ ሰውየው ላይ የሚደርሰውን ቅጣት ከማሰብ ይልቅ መጀመሪያ በተቻለ አቅም ለዛ ሊያጋልጡ ከሚችሉ ነገሮች ራሷን ልትጠብቅ ያስፈልጋል። ተፈጽሞ ሲገኝም ደግሞ ብልሃት ያስፈልጋል። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ማስረጃ ወዲያውኑ አለማቅረብ፣ ወደ ህክምና ተቋማት ወዲያው አለመሄድ፣ ለፖሊስ የተፈጠረውን አለማሳወቅ፣ ቅደም ተከተሉን ባለማወቅ የሚዘነጉ ነገሮች መብትን እስከማሳጣት ሊያደርሱ ይችላሉ። ስለዚህ ብልሃት ብዙ ድርሻ አለው።

አዲስ ዘመን:- ማህበሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ያለው በየትኛው ላይ ነው?

ወይዘሮ ቤተልሔም:- እንደ ማኅበር በብዛት እየሠራን ያለነው ጥቃትን በተመለከተ ነው። በተለይ ደግሞ ወሲባዊ ትንኮሳን በተመለከተ የህዝቡ ግንዛቤ ከፍ እንዲል ነው የምንፈልገው። እኛ አገር ባለው የህግ ሁኔታ ወሲባዊ ትንኮሳ የተዳሰሰ አይደለም። ወሲባዊ ትንኮሳ ስንል አስገድዶ መድፈርና ከፍ ያሉ ጥፋቶች ላይ እንጂ «ለከፋ» የሚባለው እንደቀላልና እንደ ንግግር መክፈቻ የሚታይ ነው። አለባበስ ላይ ያለው አመለካከት ራሱ፣ ሴቶች ራሳቸው ናቸው ራሳቸውን የሚያጋልጡት እየተባለ የሚያሳስት፣ ከደረሰው ጥቃት በላይ ጥቃት አድራጊዎችን ሊከላከል የሚችል የግል አስተያየት ነው።

የኅብረሰተቡ አመለካከት መስለው ነገር ግን ህግን በተመለከተና የሴቶችን መብት ከማስከበር አንጻር ትልቅ ሚና የሚጫወቱና መብታቸው እንዳይከበር የሚያደርጉ ስለሆኑ ይህን በተመለከተ መገናኛ ብዙኅን ላይ በደንብ ቢሠራ እላለሁ። በመገናኛ ብዙሀን «በለከፋ ተዋውቃችሁ የተጋባችሁ» እየተባለ እንደቀልድና ቀላል ነገር መታየት ሳይሆን ያለበት ትኩረት ተሰጥቶት ጾታዊ ጥቃትና ወሲባዊ ትንኮሳ ነገሮች በኅብረሰተቡ ዘንድ እውቀቱ ከፍ እንዲል የሚችልበት ሁኔታ ቢፈጠር እንላለን።

አዲስ ዘመን:- ስለሰጠሽን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።

ወይዘሮ ቤተልሔም:- እኔም አመሰግናለሁ።

 

ሊድያ ተስፋዬ

Published in ማህበራዊ
Saturday, 07 October 2017 17:28

ከፓርላማው ምን ይጠበቃል?

       

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ፤      አቶ ሞሼ ሰሙ፤                  አቶ ትዕግስቱ አወል፤          አቶ ጥላሁን እንዳሻው፤         አቶ አየለ ጫሚሶ፤

 

ኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓትን ተግባራዊ ባደረገችባቸው ያለፉት 25 ዓመታት በርካታ ስኬታማ ስራዎችን አከናወናለች። ብሄር ብሄረሰቦች መብታቸው ተከብሮ፣ በራሳቸው ቋንቋ ተምረው፣ ተዳኝተውና ክልላቸውን ራሳቸው አስተዳድረው ልማታቸውንና እድገታቸውን ያረጋገጡበት ደረጃ ላይ መድረስ ችለዋል። ለአገራቸው ሰላምና ልማት ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል። ይሄ የሆነው ግን ምንም አይነት ኮሽታ ባልታየበት ሁኔታ አይደለም። አልፎ አልፎ የሚነሱ ሰላምን የሚያደፈርሱ ችግሮችም ተስተውለዋል። እነዚህ ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ ከአምስተኛው ዙር የሶስተኛው ዓመት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምን አዲስ ነገር ይጠበቃል? በምን በምን ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይገባቸዋል የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አንዳንድ አመራሮችንና የፖለቲካ ሙሁራንን አነጋግረናል። እነሱም የሚከተለውን ይናገራሉ።

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ

«ፓርላማው ስራውን ሲጀምር በወቅታዊ ጉዳዮች ብዙ አዳዲስ ደንቦችና ህጎች ማጽደቅ ይጠበቅበታል» የሚሉት የአፍሪካ ሂውማኒተሪያን አክሽን ምክትል ፕሬዚዳንትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ ናቸው። እንደ ምሁሩ ማብራሪያ ለሁሉም ነገር ቀዳሚው የህግ የበላይነት ማስፈን ነው። በመሆኑም ባለፉት ጊዜያት በተከሰቱት ጥፋቶች የተሳተፉ ግለሰቦችም ሆኑ ነገሩን በማስነሳትና በማባባስ ላይ የነበሩት እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሆነው ስራቸውን በአግባቡ ያልተወጡት ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ መፈጠር አለበት።

ለዚህም የፓርላማው ስራ አስፈጻሚ አካል የፓርላማ ኮሚቴ መድቦ ጉዳዩን እንዲከታተል ማድረግ ይጠበቅበታል። በተጨማሪም ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት እንደ ሰብአዊ መብት፣ እንባ ጠባቂ ያሉትን ሪፖርት አዳምጦ ፓርላማው አዲስ መመሪያዎችን ማውጣት ይችላል። ከዚህም ባለፈ በሚካሄዱ ግምገማዎች ችግር አለባቸው የሚባሉና ሆን ብለው ሀገሪቱን ወደ ችግር የመሩ የስራ ኃላፊዎች ከተገኙ ሰዎቹ ችግር እየፈጠሩ አልያም እያባባሱ እንደሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሳሰብ እርምጃ እንዲወሰዱባቸው፤ ክልሎቹ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ ቢሆንም ጉዳዩ ከሀገር ደህንነትና ሰላም ጋር የሚያያዝ በመሆኑ በፌደራል የሚወሰዱ እርምጃ እንዲወሰዱ ማድረግም ይጠበቅ በታል።

ምሁሩ ጨምረው እንዳብራሩት፤ የጎሳ ግጭቶች አዲስ የተፈጠሩ ሳይሆኑ ለዘመናት የኖሩ ናቸው። በተለይ የውሃ ምንጭ፣ የግጦሽና የእርሻ መሬት በመፈለግ እንዲሁም ከብት በመቀማማት ከዚህ ቀደምም ይፈጠሩ ነበር። እነዚህ ግጭቶች ድሮ ከቀስትና ከጦር በዘለለ መሳሪያ የሚካሄዱ አልነበሩም። አሁን በአውቶማቲክ መሳሪያም ጭምር ነው የተጀመሩት። እንደእነዚህ አይነት መሳሪያዎች ደግሞ በህግ አስከባሪዎች እጅ ላይ ብቻ ነው መያዝ ያለባቸው። እነሱም ቢሆኑ ለህግ ተገዢ ካልሆኑ በህግ አግባብ የሚነጠቁበት ሁኔታ መፈጠር አለበት።

በተለይ አሁን የተከሰተው አይነት የብሄር ብሄረሰቦች ጎራ ለይቶና በመንግስት ታጣቂ ሀይሎች መካከል ጭምር የተደረገ ጦርነት በታሪካችን ታይቶም ተሰምቶም የሚታወቅ አይደለም፤ተገቢም አይደለም። ያለፈ ታሪካችን የሚያሳየው የውጪ ጠላት ሲመጣ ሁሉም ተባብሮ የመከላከልና የአንድነት እንቅስቃሴ አካሄድን ነበር። አሁንም ማስቀጠልም ያለብን ይህንኑ ነው። በተለይ አንድን ህዝብ የዚህ ክልል ነዋሪ አይደላችሁም ብሎ ማባረር የኢትዮጵያዊነት መብታቸውንም መግፈፍ ነው። በመሆኑም ፓርላማው ይህንን በጥሞና ተመልክቶ ተገቢና ፈጣን ውሳኔ ማስተላለፍ ይጠበቅበታል።

ከሁሉም በላይ ህዝቡ ኢትዮጵያዊነትን ለማስፈን በክልል ደረጃ አንድ ጎሳ ከሌላ ጎሳ እየተባለ በሚዲያዎችም ጭምር የሚነገረው በፍጥነት መቆም እንዳለበት ይመክራሉ። ክልሎችም ኢትዮጵያዊነትን በመያዝ እነሱም የኢትዮጵያ ማእከል መሆናቸውን እንዲገነዘቡ ማድረግ ሌላው የፓርላማው ስራ ሊሆን እንደሚገባም ምሁሩ አስገንዝበዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር የማነ ዘርአይ

በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የማነ ዘርአይ እንዳሉት፤ በተያዘው አመት ፓርላማው ስራውን ሲጀምር በዋናነት በሁለት ጉዳዮች ላይ ሊያተኩር ይገባል ይላሉ። የመጀመሪያው ባለፉት ሁለት አመታት እንደ ሀገር የገጠሙ ችግሮች አሉ። ከእነዚህ ችግሮች የህግ ውሳኔ የሚፈልጉ ጉዳዮች ምንድን ናቸው በማለት ለይቶ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስቱን ለማስፈጸም የወጡ ዝርዝር አዋጆችና ደንቦችን ችግር ያለባቸውና ግልጽ ያልሆኑትን በመለየት እንዲሻሻሉ መስራት ይጠበቅበታል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የዴሞክራሲያዊ ስርአቱን ለወቅቱ በሚመች መልኩ ማድረግና የምርጫ ህጉን ማሻሻልን ጨምሮ ባለፈው አመትም የተገቡ ቃሎች ዝርዝር ህጎችን የሚመለከቱ ናቸው። እነዚህ ጉዳዮች አስፈጻሚውን ብቻ የሚመለከቱ ሳይሆኑ በዋናነት ፓርላማውን የሚመለከቱ በመሆናቸው፤እነዚህን ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ በመፈተሽ ውሳኔ ማሳለፍ ያስፈልጋል።

በሁለተኛ ደረጃ ባለፈው አመት መሪው ፓርቲ ኢህአዴግም ሆነ መንግስት የተሀድሶ እንቅስቃሴ አድርገዋል። ተሀድሶው የመጨረሻ ውጤት የሚኖረው የህግ ማእቀፍና የአወቃቀር ለውጦችና ዝርዝር አፈጻፀሞች ሲካተቱ ነው። በመሆኑም ፓርላማው በተሀድሶው የተመዘገቡ ለውጦች ወደ ህዝቡ እንዲደርሱ ለማስቻል የተሀድሶው እንቅስቃሴ ወደ ህግ መተግበር አለበት። በተለይ በአመቱ መጀመሪያ የሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ ትኩረት አድርገው እርምጃ የሚወስዱባቸውና እቅድም የሚቀመጥባቸው ሊሆኑ ይገባል።

በሌላ በኩል ኪራይ ሰብሳቢነት በሀገሪቱ ባለፉት አምስት አመታት ሲነሳ የነበረ ችግር ነው። በእውነትም ከሀገሪቷ የኢኮኖሚ እድገትና ከምትከተለው ስርአት አንጻር ይህ ችግር ለሀገሪቷ ትልቅ አደጋ ነው። ኪራይ ሰብሳቢነት አለ ማለት ደግሞ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ ማለት ነው። ለዚህም ባለፈው አመት አጀንዳ ተይዞ ሊሰራ የተቀመጠ ጉዳይ አለ። ይሄን በአንድ ጊዜ ማቃለል ባይቻልም ገምግሞ ለቀጣይ ማቀድ ይገባል።

የስራ አጥነት ችግርንም ለመቅረፍ ገንዘብ በመመደብ የተጀመረው ስራ እንዳለ ሆኖ ፓርላማው ተቋማዊ በሆነ መንገድ በዘላቂነት እንዲፈታ ምን ብናደርግ ነው ኢኮኖሚውን የምናንቀሳቀስው በሚለው ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊወያይ ይገባል። ለዚህም ጊዜውን የጠበቀ የፖሊሲ ማእቀፍ መዘጋጀት አለበት። የትምህርት ተቋማትንም ተማሪዎችን አስመርቆ ከማስወጣት ባለፈ ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ የሚሰሩትን ስራዎች ተከታትሎ መገምገም ይጠበቅበታል።

አቶ ሙሼ ሰሙ

ቀድሞ የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) አመራርና አባል የነበሩ አሁን ከፓርቲው ወጥተዋል። አቶ ሙሼ ሰሙ እንደሚናገሩት ባለፈው አመት በተከታታይ በተፈጠሩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በሀገሪቱ ከንብረት ውድመት እስከ ሰው ህይወት መጥፋት የደረሱ ችግሮች ተከስተዋል። ዜጎችም እንደ ሀገር ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብታቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል። እነዚህ ችግሮች አሁንም እየተከሰቱ ያሉ በመሆናቸው ፓርላማው በቅድሚያ በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት።

ሰላምና መረጋጋት በሌለበት ስለ ልማትም ሆነ ዲሞክራሲ አልያም የሀገር ብልፅግና ማውራት አይቻልም። አሁንም ቢሆን ነገሮች የበረዱና የሰከኑ ይምሰሉ እንጂ መልክና ገጽታቸው እየተለዋወጠ ግጭቶቹ እየቀጠሉ ዜጎችም ለችግር እየተጋለጡ ናቸው። በመሆኑም ዜጎች ህገ መንግስቱ ባስቀመጠላቸው መብት መሰረት በየትኛውም ቦታ ሰርተው አምርተውና ንብረት አፍርተው የመኖር መብታቸው እንዲረጋጋጥ መስራት ከፓርላማው ይጠበቃል።

አቶ ሙሼ በፓርላማው መሰራት ይገባዋል ያሉትንም መፍትሄ ሲጠቁሙ፤ፓርላማው ስራውን ሲጀምር ጉዳዩ የሚመለከተውንና ያገባኛል የሚል ማንኛውንም አካል የማወያያት ስራ ሊሰራ ይገባል። ጥያቄ አለን መልስ እንፈልጋለን ለሚሉ በሙሉ የጉዳዩ ብቻ ሳይሆን የመፍትሄውም አካል በማድረግ ምላሽ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች መስራት አለበት። በጉዳዩ ተሳትፎ የነበራቸውና ጥያቄ ያነሱ መልስ የሚሹ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎቹን በማቅረብ ሰፊ ውይይትና ክርክር ተካሂዶባቸው አማራጭ ሀሳቦች የሚስተናገዱባቸው እድሎች የሚፈጠሩበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት ይላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ በ2010.ም በሚካሄደው የማሟያ ምርጫ ውጤቱ የታወቀ ምርጫ እንዳይካሄድ፤የተስተካከለ ምህዳር እንዲኖርና ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተሳታፊ እንዲሆኑ፤ፓርላማው ከኢህአዴግም በላይ የህዝብ ተጠሪነትና ተጠያቂነት ስላለበት ምህዳሩ በሚስተካከልበት ሁኔታ ላይ መስራት ይጠበቅበታል። ይሄን በማድረግ በየወቅቱ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው የሚለውን እንዲፈትሽና ምላሽ እንዲሰጥ ያስችለዋል። እነዚህ ሁኔታዎች ለሀገሪቱ መረጋጋትና ሰላም መነሻ በመሆናቸውና የፓርላማ አባላቱም በፓርላማ ለመቀጠል የሚያስችላቸውን እድል የሚያገኙበት በመሆኑ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩባቸው ይገባል ብለዋል።

አቶ ትዕግስቱ አወል

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ትእግስቱ አወሉ በበኩላቸው የፖለቲካ ተሳትፎ ምህዳሩን ለማስፋት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የተጀመረው ድርድር ተጠናቆ ወደ ተግባር እንዲቀየር ፓርላማው መስራት አለበት ይላሉ። እንደ ሊቀመንበሩ ገለጻ እስካሁን ባለው ሂደት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በተደረገው ድርድር በአንድ ህግ ላይ ከስምምነት ተደርሷል። ሁለተኛውንም ህግ ከስምምነት ላይ ለመድረስ እየተሰራ ነው።

ይህንን መሰረት በማድረግ ፓርላማው በፍጥነት ስምምነት የሚደርስባቸውን ጉዳዮች ህግ አድርጎ በማውጣትና በማፅደቅ ምህዳሩ እንዲሰፋና አዲሱ የምርጫ ስርአት ፀድቆ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ተተግብሮ እንዲሞከር ሊሰራ ይገባል። ፓርላማው ይህንን ካደረገ በምርጫ ሂደት ያሉትን ጠንካራና ደካማ ጎኖች በመፈተሽ በ2012 .ም በሚኖረው ብሄራዊ ምርጫ የተሻለ ተሳትፎ እንዲኖር ማድረግ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር ይቻላል። ይሄ ካልሆነና ከዚህ ቀደም በነበረው የምርጫ ስርአት የምንቀጥል ከሆነ ምርጫው አሳታፊ ካለመሆኑ ባሻገር ውጤቱም የታወቀ እንደሆነ የሚቀጥል ይሆናል። ይሄ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ህልውና ብቻ ሳይሆን የህዝብን በምርጫ ያለውን ተሳትፎም የሚያቀዛቅዝ ነው የሚሆነው።

አቶ ጥላሁን እንደሻው

« በሀገሪቱ ያለው ቀዳሚውና አንገብጋቢው ጉዳይ ፓርላማውም ሊሰራበት የሚገባው የህዝቡ የሰላምና የደህንነት ጉዳይ ነው። ፓርላማው ስራውን ሲጀምር የሀገሪቱ ዜጎች በሰላም ሰርተው መኖር የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማስቻል ይጠበቅበታል» ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዲፓ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጥላሁን እንደሻው ናቸው። እንደምክትል ሊቀመንበሩ ማብራሪያ በአሁኑ ወቅት በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያለው የሰላም ሁኔታ አስጊ ነው። በተለይ በክልሎች ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ወገኖች ለብዙ ችግሮች ተጋልጠው ይገኛሉ። እነዚህ ዜጎች የህግ ከለላና የመንግስትን አለሁ ባይነት ይፈልጋሉ፤ ይጠብቃሉም። በአንዳንድ አካባቢዎች ኢትዮጵያዊ የሆኑ ዜጎች ከሌላ ሀገር እንደ መጣ ሁሉ ከኖሩበት ቦታ ሲባረሩ ይታያሉ። ይሄ ብሄራዊ ህልውናን ፈተና ላይ የሚጥል ትልቅ አደጋ ነው።

በመሆኑም የችግሮቹን መነሻ በራሱ በመንግስት አካላትም በኩል ያሉትን ጨምሮ በመለየት ተጨባጭ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ያስፈልጋል። ፓርላማው የመንግስት አካላትን በበላይነት የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለበት አካል እንደመሆኑም ማንኛውንም አስፈጻሚ አካል የመቆጣጠር ስራውን በስራ ዘመኑ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። እንደ ፓርላማም በሀገሪቱ እየተከሰቱ ባሉ አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ አጀንዳ አስይዞ መነጋገር ይጠበቅበታል። ጉዳዩ የሚመለከታቸውንም አካላት ጠርቶ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ መጠየቅና ተገቢ ማስተካከያ የማያደርጉ ካሉም ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው የማድረግ ኃላፊነትም አለበት።

ከመልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነት ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ እለት ከእለት እየጨመሩ የመጡትም ችግሮች ከጸረ ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ባህሪ የመነጩ ናቸው። አሁን እየተከሰቱ ላሉ አንዳንድ ችግሮችም መነሻቸው የመልካም አስተዳደር እጦትና የኪራይ ሰብሳቢነት መንሰራፋት ናቸው። አሁን ያለው አደረጃጀት ዜጎች ስራ የሚያገኙት ባላቸው የዜግነት መብት፣ የስራ ብቃትና የሞያ ችሎታ ሳይሆን በፖለቲካ ታማኝነትን ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም አሁንም በስራ ፈጠራ የሚሰማራውና ለስራው የተመደበው ገንዘብ ለኢህአዲግ ደጋፊዎች ብቻ እንዳይሆን ከፓርቲ ወገንተኝነት ፀድቶ ነጻ የስራ እድል እንዲፈጠር ፓርላማው ተከታትሎ መስራት አለበት። ይሄ አካሄድ ደግሞ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን አያስችልም። በመሆኑም ፓርላማው የገዢው ፓርቲ አካል እንደመሆኑ ሀገሪቷ ወደ ዳበረ ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንድትመለስ መስራት አለበት።

በሌላ በኩል በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እየተደረገ ያለውም ድርድር ሳይሆን ውይይትና ምክክር ነው የሚሉት አቶ ጥላሁን እንደ ፓርቲ በአግባቡ ድርድር እንዲደረግ ያቀረቡት ሀሳብ ተቀባይነት አላገኘም። በመሆኑም መጀመሪያ ትክክለኛ ድርድር እንዲካሄድ ፓርላማው ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠበቅበታል። ገዢው ፓርቲ በገለልተኛ አደራዳሪዎች አማካይነት መሰረታዊና ችግር ፈቺ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከትክክለኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መደራደር አለበት። በዚህም በሀገሪቱ ትክክለኛ ምርጫ የሚካሄድበትና ህዝቡ በነጻነት ድምጹን የሚሰጥበት ሁኔታ እንዲፈጠር መሰራት አለበት። በገለልተኛ የምርጫ አስተዳደር ምርጫ የሚካሄድበት ሁኔታ እንዲፈጠር መስራት ይገባል ባይ ናቸው።

ከዚህ በፊት በተካሄዱት ምርጫዎች እንደታየው ለገዢ ፓርቲ ሁሉንም ነገሮች ጠቅልሎ የሰጠ የምርጫ አስተዳደር ባለበት ሁኔታ ትክክለኛ ምርጫ ሊካሄድ ስለማይችል፣ ከምርጫው በፊት ሀቀኛ ድርድር መካሄድ አለበት። አሁን ያለውን ግን ድርድር ነው ማለት አንችልም። ፓርላማው እስካሁን ባለው ሂደት ገዢውን ፓርቲ እንዲህ አድርግ ብሎ አመራር ሰጥቶ አያውቅም። ነገር ግን ገዢውንም ፓርቲ አስፈጻሚ አካላትም የሚሰሯቸውን ስራዎች በጥልቀት በመገምገም ስህተቶች ላይ ተችተው ማስተካከል ይጠበቅባ ቸዋል። ከዘንድሮው ፓርላማም የዚህ አይነት አዲስ እንቅስቃሴ እንጠብቃለን ብለዋል።

አቶ አየለ ጫሚሶ

«እኛ ብቻ ሳንሆን ህዝቡም ከፓርላማው የዘንድሮ የስራ ዘመን ብዙ ይጠብቃል፤ ፓርላማው የሚሰራቸው የተለመዱ ስራዎች እንደተጠበቁ ሆነውም በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ማተኮር ግን አለበት» የሚሉት የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ አየለ ጫሚሶ ናቸው። አቶ አየለ እንደሚናገሩት ህዝብ የሚፈልገው፤ ፓርላማውም ሊያውቀው የሚገባውና ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት ያለበት ጉዳይ በሀገሪቷ እየተከሰተ ያለው የእርስ በእርስ ግጭት ቆሞ ሰላም የሚፈጠርበትና ሀገር ለዘለቄታው የምትረጋጋበት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው። በአሁኑ ወቅት የሀገር አንድነትን የሚያናጋ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። እነዚህ ግጭቶች ከሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጪም ባሉ ስውር እጆች ግፊትና ንቃተ ህሊና በሌላቸው ሰዎች አነሳሽነት የሚቀሰቀሱ ናቸው። ይሄ ደግሞ የሀገር ሰላም ጉዳይ እንደመሆኑ ፓርላማው የተፈጠረው ችግር በቁጥጥር ስር ውሎ የህዝቦች ሰላም የሚረጋገጥበት ሁኔታ እንዲፈጠር የመስራት ግዴታ አለበት።

ከዚህም ባለፈ ፓርላማው በቅርቡ በተከሰቱትና ለበርካታ ዜጎች ህልፈት የዳረጉ ግጭቶች ውስጥ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ አንዳንድ አካላት እጅ አለበት የሚል ጥርጣሬ አለ። ይሄንን አጣርቶ በአስፈጻሚ አካል ላይ ጥብቅ ግምገማ በማካሄድ ተገቢውን ቁጥጥርና እርምጃ ሊወስድ ይገባል። እንዲሁም እንደ ፓርላማ ህገ መንግስቱ በሚያዘውና በተሰጠው አዋጅና ስልጣን መሰረት በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች የሚሾሙ አስፈጻሚዎች ለመንግስት፣ ለህገመንግስቱና ለህዝቡ ታማኝ የሆኑ እንዲሆኑ፤ከዚህም ሌላ ድብቅ አጀንዳ ካላቸውና አገርን ለመበታተንና ለማፈራረስ ከሚሰሩ ጋር የማያብሩ መሆናቸውን የማረጋገጥ ስራ ሊሰራ ይገባል።

በተያያዘ ሀገሪቱ እያካሄደች ያለውን ልማት ለማደናቀፍ የሚሞክሩ የውጪም ሆነ የውስጥ ኃይሎች እንዲሁም አንዳንድ የጎረቤት ሀገራት መኖራቸው ይታወቃል። በመሆኑም የሀገሪቱ ዳር ድንበር እንዲጠበቅ በሚደረጉ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባቸዋል።

በሙስናውም በኩል ለሀገር ልማት የሚውል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በአንዳንድ ግለሰቦች እየተዘረፈ ይገኛል። እነዚህን ሰዎች ለህግ በማቅረብ ተገቢውንና አስተማሪ ሊሆን የሚችል ቅጣት እንዲወሰድ ማድረግም ይጠበቃል።

በሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች በየአመቱ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች እያስመረቁ በማውጣት ላይ ቢሆኑም አብዛኞዎቹ ስራ አጦች ሆነዋል። ለዚህም የፈዴራል መንግስት ብቻ ሳይሆን ክልሎችም ጭምር የየራሳቸውን ተጨባጭ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በማስፋፋትና በጀት በመመደብ ዜጎች ስራአጥ በመሆን ወደ አመጽና ሌሎች ተግባራት እንዳይገፋፋ ለማድረግ እንዲሰሩ ፓርላማው ማሳሰብ አለበት ብለዋል። ባለፈው አመት በፌደራል መንግስት የተመደበውም ከፍተኛ መጠን ያለው የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ እስከተጠናቀቀው አመት መጨረሻ ወጣቶቹ ሰልጥነው ተዘጋጅተው ቢቀመጡም አብዛኞቹ ወደስራ አልገቡም።

በመሆኑም አሁንም ፓርላማው በጀቱ መበጀቱን ብቻ ሳይሆን ያለበትንም ሁኔታ በመከታተል ወደ ተግባር የሚገባበትን ሁኔታ ማመቻቸት ሌላው የአመቱ ቁልፍ ተግባሩ ሊያደርግ ይገባል። ይሄ ካልሆነ ገንዘቡ ወደ ጥቂቶች ኪስ በመግባት ህዝብን ለሌላ አመጽ ለሌላ ችግር ይዳርጋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ የሴቶች ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት እያደገ ቢሆንም ዛሬም ሀገሪቷ በርካታ ሴቶች በተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ውስጥ የሚገኙባት በመሆኑ እንደዚህ ትልልቅ ሀገር አቀፍ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ሲካሄዱ ከወረቀት በዘለለ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት በተግባር መረጋገጡን መፈተሽ ይጠበቃል።

በአጠቃላይ በራሳቸው ስራ ለሚፈጥሩ የተጀመረውን ድጋፍ በማጠናከር መንግስትም በየተቋማቱ የስራ እድል በመፍጠር የብጥብጥ ምንጭ የሆነውን ስራ አጥነትን ለመቀነስ መሰራት አለበት። ፓርላማው በየወቅቱ የህዝብን ጥያቄ እያዳመጠ ምላሽ የሚሰጥበት እንጂ በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እየታወጀ ችግሮች ብቻ የሚፈቱባት እንዳይሆን ከፓርላማው ብዙ ይጠበቃል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 

ራስወርቅ ሙሉጌታ

 

 

Published in ፖለቲካ

የውሀ አካላት በተለይ ደግሞ ሀይቆቻችን ከብክለትና ብክነት ጋር ተያይዞ አደጋ ውስጥ ወድቀዋል። ትላልቅ ሀይቆችም እየጠፉ ናቸው። ለመሆኑ ለሀይቆች ብክለትና ብክነት ዋነኛው ችግር ምንድን ነው? መፍትሄውስ? ስንል በኢትዮጵያ የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስትቲዩት የአካባቢ ብክለት አያያዝ ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና ተመራማሪ ከሆኑት ከአቶ የአለምሰው አዴላ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገናል።

አዲስ ዘመን፡- አንድ የውሀ አካል ወይም ሀይቅ ተበከለ የሚባለው ምን ሲሆን ነው?

አቶ የአለምሰው፡- አንድ ስርዓተ ምህዳር ችግሮችን የሚቋቋምበት ተፈጥሯዊ አቅም ወይም ደረጃ አለው። ውሀም ችግሮችን መቋቋም የሚችልበት የተፈጥሮ አቅም አለው። ለምሳሌ አንድ በርሜል መርዛማ ኬሚካል ወደ ሀይቅ ቢገባ በሰፊው የውሀ አካል ውስጥ ይዋሀዳል። የውሀው መጠን ከፍተኛ ስለሆነ የመቋቋም አቅም ይኖረዋል። ውሀውን የጠጣው ሰው ላይሞት ይችላል። አሳውንም ላይገድለው ይችላል። በሰፊው የውሀ አካል ተፅእኖው ይቀንሳል ማለት ነው።

ሌላው ደግሞ እዛው ስርዓተ ምህዳር ውስጥ አፈር አለ፤ በአይን የማይታዩም የሚታዩም ተክሎች አሉ። ኬሚካሉን ላያቸው ላይ አጣብቀው ይይዙታል፤ በተለይ አፈር ራሱን የቻለ አንድ ማጣሪያ ነው። ስለዚህ ውሀውን አሳዎች፥ሰዎችና ከብቶች ሲጠቀሙት ጉዳቱ ወዲያው አይታወቅም። ይህ የሆነው ያ ስርዓተ ምህዳር አደጋውን ወይም ችግሩን የመቋቋም ተፈጥሯዊ አቅም ስላለው ነው። አሁን ውሀው ተበከለ የምንለው የመቋቋም አቅሙን መጠን አልፎ የተገኘ የውሀ አካል የሚጠቀሙትን እንስሳትም ሆነ ሰው ጉዳት ሲያስተናግድና ተፅእኖው ሲታይ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ለኢትዮጵያ ሀይቆች ዋና ዋና የብክለት መንስኤዎች ምንድን ናቸው?

አቶ የአለምሰው፡- በዋነኛነት ብክለት ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ነው። ሰው ሰራሽ የምንለው ሰው በተፈጥሮው የተሻለ ህይወት ፍለጋ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የሚያመጣውና የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርገው የተሻለ ህይወት ፍለጋ ነው። ስለዚህ ፍላጎታችንን ለማሟላት በምናደርገው ሂደት ውስጥ አካባቢ ላይ ተፅእኖ ይፈጠራል፤ስርዓተ ምህዳሩ ይረበሻል፤ይሄ የሰው ልጆች የቀን ተቀን እንቅስቃሴ የሚያመጣው ሰው ሰራሽ ብክለት ተብሎ ይጠራል።

ተፈጥሯዊ ብክለት ደግሞ አለ። የመሬት መንቀጥቀጥ፥ በዓይን የማይታይ የመሬት ውስጥ እንቅስቃሴ ሲከሰት የሚለቀቁ ማዕድናት አሉ። እሳተ ገሞራ ሲፈነዳ፣ ሀሪኬይን ሱናሜ ሲነሱ ብክለትን ያስከትላሉ። ወደ እኛ አገር ስንመጣ በተለይ ሰው ሰራሹ ብክለት በዝቶ ይታያል። ይሄ ደግሞ ከፖሊሲ ክትትልና ቁጥጥር ጋር ይገናኛል። የሰው ሰራሽ ብክለትን ለመቋቋም ህጉ አለ፤ ፖሊሲም አለ፤በአተገባበር ግን ችግር አለ።

በአደጉት አገራት አካባቢ ላይ የሚደርስን ጉዳት ቀድመው ማወቅና ማስተካከል ስለቻሉ ያስቀመጧቸው ህጎችና ህጎቹን የሚተገብሩበት አካሄድ በጣም ጥብቅ ነው። በእነዚህ አገራት ሰው ሰራሽ ብክለት ቢኖርም በህግና በቴክኖሎጂ ተቆጣጥረውታል።

ለምሳሌ አቢያታ ሻላ ሀይቅን ላንሳልህ። ስለዚህ ሀይቅ ብዙ ተብሏል። ከዛሬ 11 እና 12 ዓመት በፊት ለጉብኝት በሄድኩበት ወቅት የውሀው መጠን ሀይቁ ከነበረበት ይዞታ 17 ኪሎ ሜትር ሸሽቶ ነበር። በአሁኑ ወቅት ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ ሸሽቷል እየተባለ ነው። ይህን ከብክነት ጋር ማያያዝ ይቻላል።

በእዚሁ ሀይቅ አካባቢ አንዱ የብክነት ምንጭ የሶዳ አሽ ፋብሪካ መኖር ነው። ይህ ፋብሪካ የሀይቁን ውሀ በቱቦ ስቦ ለፋብሪካው ይጠቀማል። ይህን ውሀ ስበህ ስትጠቀም መልሰህ ውሀ የምትተካበት መንገድ ሊኖር ይገባል። ይህ በቀጥታ ከፖሊሲ ጋር ይገናኛል። የውሀ አካላትን በተለይ ደግሞ ሀይቆችን እንድትጠብቅ የሚያስገድድ ህግ፤ፖሊሲ አለ። እዚህ ጋር ያለውን በተግባር ሲታይ ምን እየተከናወነ ነው? ብለህ መጠየቅ አለብህ። ያለአግባብ እየተጠቀሙ የህግ ተጠያቂ የሚያደርግ አካል የለም። ስለዚህ ህጉን አላስጠበክም ማለት ነው። ስለዚህ ለእኛ አገር ሀይቆች ብክለት በዋነኛነት ሰው ሰራሽ ነው። ይህን በስምጥ ሸለቆ አካባቢ ካሉት ፋብሪካዎች ጋር አያይዞ ማየት ይቻላል። ኢንዱስትሪዎች የሚያስወግዱትን ዝቃጭ አጣርተው የሚለቁበት አሰራርም ሆነ ቴክኖሎጂ አይጠቀሙም።

አዲስ ዘመን፡- ፋብሪካዎች ዝቃጮቻቸ ውን አጣርተው እንዲለቁ የሚደረገው ቁጥጥር እና ክትትል ከየት መጀመር አለበት?

አቶ የአለምሰው፡- እያንዳንዱ የልማት ፕሮጀክት ወደ መሬት ከመውረዱ በፊት የአካባቢ ተፅእኖ ግምገማ መስራት አለበት። አንድ ፋብሪካ ይዞት የሚመጣው የልማት ፕሮጀክት መልካም አጋጣሚ ቢሆንም ፕሮጀክቱ ወደ መሬት ሲወርድ ማህበረሰቡና አካባቢው ላይ የሚኖረው ተፅእኖ መታወቅና መለየት አለበት። ይህን ተከትሎ ምን አይነት ዘዴን መከተል አለበት የሚለው ሊመለስ ይገባል። የፕሮጀክቱን ጉዳት መቀነስ ይገባል። ይሄ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ከመሆኑ አስቀድሞ የሚፈፀም ነው። የልማት ፕሮጀክቱ ይቁም አይባልም። ይልቁኑ ተፅእኖውን የሚቀንስበትን አማራጮች አሳይቶ፤ፕሮጀክቱም ተገምግሞ ሲፀድቅ ነው ወደ መሬት የሚወርደው። ስለዚህ አሁን ያሉት ትልልቅ ፋብሪካዎች ዝቃጫቸውን ሳያጣሩ የሚለቁ ኩባንያዎች ፕሮጀክቱን ወደ መሬት ሲያወርዱት ፍቃድ ተሰጥቷቸው ነው። የአካባቢ ተፅእኖ ግምገማ ፍቃድ አላቸው።

በዚህ ረገድ የእኛ ተቋም ያጠናው ጥናት አለ። አብዛኞቹ የአካባቢ ተፅእኖ ግምገማ የተሰጣቸው ፕሮጀክቶች እጅግ አሳፋሪ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በዚህ ደረጃ ሆነው እንዴት ፍቃድ ተሰጣቸው? ከፍተኛ ብክለት በሚያስከትሉበት ደረጃ ላይ እያሉ ፍቃዱን እንዴት አገኙ ስትል የትኛውም ዘርፍ ላይ የምታየው የኪራይ ሰብሳቢነት አባዜ በከፍተኛ ሁኔታ አለ።

ባለሀብቱ ፋብሪካ ሲያስገነባ ከፋብሪካ የሚወጣን ቆሻሻ አጣርቶ ወደ አካባቢው መላክ አለበት። ይሄ ማጣሪያ የሚገነባበት ወጪ ትልቅ ነው፤ ምናልባትም የፋብሪካውን ግማሽ ወይም ተቀራራቢ ዋጋ ሊያወጣ ነው። ስለዚህ ፕሮጀክቱ ሳይፀድቅለት በጓሮ በር (ሙስና ፈፅሞ) ፋብሪካው እውን ያደርጋል። ፋብሪካውም ስራውን ሲጀምር የኢንዱስትሪውን ቆሻሻ ወደ አቅራቢያው ወንዝ ወይም ሀይቅ ይለቃል። በኋላም ተበከለ እያልን እንጮሀለን።

ስለዚህ ችግሩ በጣም የተያያዘ ነው። ፋብሪካዎቹ መሬት ከመውረዳቸው በፊት ያለ አሰራር ነው። ሀይቅ ላይ የምታነሳት ብክለት ፕሮጀክቱ ከፀደቀም በኋላ ቁጥጥር የሚደረግበት ነው። ተጨባጭ ምሳሌ ላንሳልህ፤ የማጣሪያ ስርዓት ያላቸው ፋብሪካዎች አሉ። ቁጥጥር ታደርጋለህ እንጂ ዘበኛ አታቆምም። መንግስት ይህ ፋብሪካ ቆሻሻ እያጣራ ነው ብሎ በየቀኑ አይቆጣ ጠርም። የኃላፊነት ስሜት ያስፈልጋል። ዋናው ስራ ኦዲት ማድረግ፣ በድንገት የሚደረግ ቁጥጥር ነው።

ይህን ለማድረግ እንኳ ትልቅ ችግር አለ። ቁጥጥር ለማድረግ ስትነሳ አስቀድሞ መረጃ ይደርሳቸዋል። በዚህ ረገድ የመድሀኒትና ምግብ ቁጥጥር ባለስልጣን ከተማ ውስጥ ቁጥጥር ሊጀምር ሲል ፋርማሲዎች በሙሉ ጥንቃቄ አድርገው ይጠብቃሉ። ያልተፈቀደ መድሀኒት ያሸሻሉ፤ይሰውራሉ። በተመሳሳይ ተቆጣጣሪዎችን ይዘህ፤ የውሀ ናሙና ወስደህ በአግባቡ እያጣሩ ነው ወይ ብለህ ቁጥጥር ስትጀምር፤የሚያጣራውን ማሽን ወይም ቴክኖሎጂ እንዲሰራ ያደርጉታል።አንተ ሄደህ በናሙናው መሰረት ስታጣራ፤ እውነትም እያጣሩ ነው። እግርህ ከዚያው እንደወጣ እያጣሩ መልቀቁን ያቋርጣሉ። ስለዚህ ሀይቆች ጋር የምታያቸው ከኢንዱስትሪ ጋር ተያይዘው ያሉት ብክለቶች ብዙ ውስብስብ ችግሮች ናቸው። ይህ አንዱ የብክለቱ መንገድ ነው።

ሁለተኛው የብክለት ምክንያት ግብርናውን ዘመናዊ ለማድረግ ከሚሰራ ከፍተኛ የሆነ የማዳበሪያ አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ነው። እነዚህ የምንጠቀማቸው ማዳበሪያዎች በዋናነት ናይትሮጂን እና ፎስፈረስ የሚባሉ ንጥረ ነገሮችን ይይዛሉ። የአገራችንን መልክአ ምድር ስታየው እጅግ ተዳፋትና ረባዳማ ነው። በእዚህ ላይ የአርሶአደሩ በእርሻው ላይ ማዳበሪያዎቹን እንዴት መጠቀም እንዳለበት ያለው ክህሎት አነስተኛና ኋላቀር ነው።

በመሆኑም አርሶአደሩ ይህን ማዳበሪያ ማሳ ላይ ይጥለዋል፤ዝናብ ሲዘንብ ደግሞ ታጥቦ በሙሉ ወንዞቹ ውስጥ ይገባል፤ወንዙም ሀይቅ ላይ ይጥለዋል። እነዚህ ማዕድናት ሀይቅ ውስጥ ገቡ ማለት ለአልጌ /ተክል/ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። በዚህም የሚኖረው እድገት ፈጣን በመሆኑ የሀይቆቹን ስነ ምህዳራዊ ይዘት ያዛባል። ከዚህ አልፎ ሀይቁ አሳ እንዳይራባበት ያደርጋል። ምክንያቱም ከፍተኛ አልጌ ይኖርና በደለል የመሞላት እድሉን ያፋጥነዋል። ይህ ሌላው የብክለት መንገድ ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የፀረ ተባይ መድሀ ኒቶችን፣ የአረም ኬሚካል እንጠቀማለን። ይሄ የፀረ ተባይ መድሀኒት 0 ነጥብ 01 በመቶው ብቻ ነው በትክክል እፅዋቱ ጋር የሚሄደው። 99ነጥብ 9 በመቶ አካባቢው ታጥቦ የውሀ አካላት ውስጥ ይገባል። ስለዚህ ምን ያህል መጠቀም አለብኝ ብለህ በሚገባ ለይተህ ካልተገበርክ ለሀይቆች ብክለት አንዱ መንስኤ ነው የሚሆነው። እነዚህ ከእርሻ ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች ናቸው።

ሌላው ደግሞ የወባ በሽታን ለመከላከል በየመንደሩና ጎጡ ዲዲቲ ይረጫል። ይሄ ብዙ መዳረሻ ሊኖረው ቢችልም የመጨረሻው እጣ ፈንታው የውሀ አካላት ናቸው። እአአ በ2012 አካባቢ ጅማ ዞን ላይ ከአንድ ጀርመናዊ ጋር ከብዙ ወረዳዎች የፀጉር ናሙና ወስደን ጀርመን ላክነው። እዛ አካባቢ ዲዲቲ 40 ዓመት ተረጭቷል። ምርመራው ዲዲቲ ፀጉሩ ውስጡ አለ ወይስ የለም የሚለውን ለመመለስ ነው። የዲዲቲ መከማቻ ደግሞ የሰው ልጆች አካል ነው። ሰብስበን ከላክነው ፀጉር ዲዲቲ የሌለው አልተገኘም።

የሀይቅ ብክለት መንስኤዎቹ ብዙ ናቸው። ከኢንዱስትሪ፣በእርሻ ማሳያዎች ላይ ከምንጠቀማቸው ማዳበሪያዎች፣ከየቤቱ ተጠራርጎ የሚወጣ ቆሻሻም መዳረሻ የሚያደርጉት ወንዞችን ነው። አዲስ አበባ ላይ ብትወስድ ወንዝ አለ ወይ ትላለህ። ወንዝን ወንዝ የሚያደርገው በውስጡ ውሀ ሲሄድበት ነው፤ ያለው ሀቅ ግን የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ መውረጃ ነው። እነዚህ ሄደው ሄደው ያሉን ሀይቆች ውስጥ ይገባሉ። ይህ በራሱ የብክለት መንስኤ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የሀይቆች ብክነት መንስኤዎቹስ ምን ምን ናቸው?

አቶ የአለምሰው፡- ለብክነት ዋና ዋና መንስኤ የምንላቸው ከሰው ሰራሹ ጋር ብናያይዘው ደለልን አለመከላከል ነው። ሀይቆች የሚኖራቸውን ተፈጥሯዊ ውሀ የመያዝ አቅም የአፈር መሸርሸርን ባለመከላከል ሊከሰት ይችላል። ይህ ሲሆን ውሀ ባከነ ማለት ነው።

ዝዋይ ሀይቅን ብትወስድ ከዛሬ 26 ዓመት በፊት 45 እና 50ሜትር ጥልቀት ነበራቸው። አሁን 2 እና 3 ነጥብ 5 ሜትር ነው አማካይ ጥልቀታቸው። ይሄ የሚያሳየው ውሀው መባከኑን ነው። ሌላው እንደ አቢያታ ሻላ ያሉ ሀይቆችን ስትወስድ ሊጠፉ ነው። ከጎኑ ውሀውን በየጊዜው እየሳበ የሚጠቀም ፋብሪካ አለ። ፋብሪካው የሚያመርተው ኬሚካል አለ። ይህን ውሀ በወሰድከው ልክ የምትመልስለት ነገር የለም።

ለዚህ ብክነት ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት የማዕድን ውሀ ብለው የሚሸጡ ድርጅቶች ናቸው። እነዚህ ፋብሪካዎች የሚጠቀሙት የጉድጓድ ውሀ ነው። ይህ ውሀ አያልቅም ማለት አይቻልም። ሲያልቅ ግን የምትተካበት ዘዴ ሊኖርህ ይገባል። የወሰድከውን ያህል ውሀ መተካት የሚያስችል ዘዴ ያስፈልጋል። ሀይቆችም ልክ እንደዚህ ተመሳሳይ የብክነት መንስኤ አላቸው። በዋናነት ስርዓተ ምህዳሩ፣ የደን መጨፍጨፍና ከፍተኛ የመሬት መሸርሸር የውሀ ብክነትን ያስከትላል።

የአፈር መሸርሸርና የደን መጨፍጨፍ በአካባቢው ያለውን የዝናብ ባህሪ ይቀይራል። ስለዚህ ዝናብ ያገኝ የነበረው አካባቢ ደኑን በማጥፋታችን ዝናቡን አናገኘውም። ስለዚህ ዝናቡ ከሌለ ሀይቁ ላይ የምትጠብቀው የውሀ መጠን ይቀንሳል። እነዚህ ዋነኛ የብክነት መንስኤ ናቸው። በመሆኑም በደለል መሞላት አንዱ የብክነት መንስኤ ነው። የሀይቆች መበከል በራሱ ብክነት ነው። ባከነ የምትለው መጠቀም ያልቻልከውን ነው። አንድ የውሀ አካል ውስጥ ኬሚካል ከገባ እና አጣርተህ እስካልተጠቀምከው ድረስ ባክኗል።

አዲስ ዘመን፡- የሀይቆቹን ብክለትም ሆነ ብክነት ለማስቀረት ምን መሰራት አለበት?

አቶ የአለምሰው፡-ይሄ ከባድ ጥያቄ ነው። ምን መሰራት አለበት ብለን ብዙ መዘርዘር እንችላለን፤ በዋናነት ግን መሰራት ያለበት የአካባቢ ጥበቃ ነው። አንዱና ዋናው ማህበረሰብ አቀፍ ግንዛቤ መፍጠር ነው። የመጀመሪያው ስራ እውቀት ማስጨበጥ ነው። ማህበረሰቡ ሀይቁ የህይወት መሰረቴ ነው የሚለውን በተግባር ማወቅ አለበት። አሳ በማጥመድ፣ የከብቶች ግጦሽ በማጣት እያልክ ግንዛቤውን ማስተሳሰር ይገባል።

ከነዳጅና ከውሀ የትኛው ነው ውዱ ብትል ነዳጅ ነው። በተጨባጭ ግን ውሀን በነዳጅ ያህል እጥረት የምታገኘው ቢሆን ውድ የሚሆነው ውሀ ነበር። አሁን ውሀ በአእምሮአችን ዋጋ አልሰጠነውም። ዋጋው ትልቅ ነው ብለህ ማሰብ ስትጀምር ነው ለፖሊሲህም ተገዥ የምትሆነው። በዚህ ረገድ ጥሩ የሚባሉ ፖሊሲዎች አሉን፤ መሬት ስታወርደው ግን ይህን መሸከም የሚችል ንቃተ ህሊና ያለው ማህበረሰብ ያስፈልጋል። እጅ ሳይታጠቡ በመብላት «ሀበሻን ጀርም አይገድለውም» የሚል አስተሳሰብ ያለው ማህበረሰብ አለን። በ21ኛው ክፍለ ዘመን በርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ስለ እጅ መታጠብ የሚያስተምሩበት አገር ነው። ስለዚህ በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ያለን ማህበረሰብ ሀይቅ ወሳኝ ነው ብትለው ቅንጦት አደርጎ ሊያስብ ይችላል። «ተቆርጦ ይበላል፤ ዳቦ አይሆን» እያለ ይመልስልሀል። ከድህነቱ ጋር ስለሚያያዝ ስትራቴጂክ የሆነ ግንዛቤ ያስፈልጋል። ይህ ሲሳካ አንድ ፋብሪካ አካባቢን ሲጎዳ አይሆንም የሚል ማህበረሰብ ትፈጥራለህ ።

ወደ መንግስት ስትመጣ ለምሳሌ አዲስ አበባ የመፀዳጃ ቤቱ ፍሳሽ ከምን ጋር የተያያዘ ነው? ይህ የሚቀረፈው የከተማ ፕላን ላይ ከየቤቱ የሚወጣን ቆሻሻ ተቀብሎ ወደ ማጣሪያ ቴክኖሎጂዎች የሚወስድ ስርዓት መዘርጋት ሲቻል ነው። ይህን አሰራር በሁሉም የአገሪቱ ከተሞች ከተዘረጋ በዚህ ረገድ ያለው ችግር ይፈታል። እያንዳንዱ በኔትወርክ ተያይዞ አንድ ቦታ ይጣራል። ቃሊቲ አካባቢ እየተገነባ ያለው ለመፀዳጃ ቤት ብቻ ሳይሆን ከኢንዱስትሪዎችም ለሚወጣው ቆሻሻም የራሱ የሆነ ማጣሪያ አለው።ይህን ማድረግ ሲቻል ጥቅል ውጤቱ የተሻለ ይሆናል።

በግብርናውም ዘርፍ የማዳበሪያ፣የፀረ ተባይና ፀረ ወባ መድሀኒቶች አጠቃቀምን ዘመናዊ ማድረግ ይገባል። ኬሚካል ስለገባ ብቻ ምርትና ምርታማነት ይጨምራል ማለት አይደለም። የተራቆተውን የደን ሽፋን በፍጥነት መመለስ የማንችል ከሆነ የምናያቸው አብዛኞቹ የውሀ አካላት ተረት የማይሆኑበት ምንም ምክንያት የለም። ሀሮማያ ሀይቅ ሊደርቅ ነው እየተባለ ደረቀ፤ ስምጥሸለቆ ውስጥም ተመሳሳይ ነው። ሳይንስ ኢትዮጵያ ውስጥ የማይሰራበት አሜሪካ ውስጥ የሚሰራበት ምንም ምክንያት የለም፤ይሰራል።ጀርም ትናንት ገድሏል፤ ዛሬም ይገድላል። ለወደፊትም ይገድላል።ይህ በጤናው ነው፤በአካባቢ ጥበቃም ተመሳሳይ ነው። በዘርፉ የሚሰጡ እያንዳንዱ የሳይንስ ጥቆማዎች ይፈፀማሉ። እንደ ፖሊሲ ችግር የለም፤ይህን የሚያስፈፅ መው ማህበረሰቡ ግን ንቃተ ህሊና ሊኖረው ይገባል። ይህን ደግሞ በዋናነት ሊሰሩ የሚገባቸው የመገናኛ ብዙሀን ናቸው። አሁን አንተ እኔን አገኘኸኝ ነገር ግን በፅሁፍህ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን ማግኘት ትችላለህ። ይህ በእውነት እና በእርግጥ ከተሰራ ማህበረሰቡ ራሱ እንዲህ አታድርግ ፤ይህን ካደረክ እንዲህ አደርግሀለሁ የሚል ደረጃ ላይ ይደርሳል ብዬ አስባለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

አቶ የአለምሰው፡- እኔም አመሰግናለሁ።

 

ሀብታሙ ስጦታው

Published in ኢኮኖሚ

በየመን በኮሌራ ከሚሞቱ ሰዎች አብዛኞቹ ህፃናት መሆናቸው ችግሩን የባሰ አድርጐታል፤

 

የኮሌራ በሽታ በዓለም ዙሪያ ከምን ጊዜውም በላይ የተስፋፋበት ወቅት እንደሆነ ይገለፃል። የዓለም ጤና ድርጅት ገለፃ፤ በሽታው ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ የበርካቶችን ህይወት አመሰቃቅሏል። የአገራት ኢኮኖሚ መሰናክልም ሆኗል።

በተለይም ባለፈው የፈረንጆቹ 2016ና በተያዘው 2017 ወረርሽኙ በስፋት የተስተዋለባቸው አገራት የአሜሪካዋ ሃይቲን ጨምሮ የመን፤ ታንዛኒያ፤ ኮንጎና ሶማሊያ ተጠቃሽ ናቸው። አፍጋኒስታንና ኢራቅም ወረርሽኙ መከሰቱን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል።

የኮሌራ በሽታ ገዳይነቱ እየጨመረ መጥቶ አሁን ላይ በየዓመቱ በመቶ ሺ ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል። በየመን የተባባሰውን ይህን ወረርሽኝ ለመታገል እየተሰራ መሆኑ ቢገለፅም መግታት ያልተቻለበት ደረጃ ላይ ይገኛል። በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ካልተፈጠረ በበሽታው ምክንያት ህይወታቸው የሚያልፍ ህፃናትን ቁጥር መቀነስ አዳጋች እንደሆነ የህፃናት አድን ድርጅት አስታውቋል።

ከምዕራቡ ዓለም ድሃዋ አገር የምትባለው ሃይቲ ሌላኛዋ በኮሌራ የሚንገላቱ ህዝቦች ያሉባት አገር ናት። በአገሪቱ በመጀመሪያ የኮሌራ ወረርሽኝ እኤአ በ2010 በተከሰተውና የሁለት መቶ ሃያ ሺ ዜጎችን ህይወት በቀጠፈው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በኋላ ነው። በሽታው በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተከሰተ ሰባት ዓመታትን ያሳለፈ ቢሆንም አሁንም ድረስ በፍጥነት እየተስፋፋና ለብዙዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት እየሆነ ይገኛል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ በርካቶች አገሪቱን ከኮሌራ ለመታደግ እየሰሩ እንደሆነ ቢገለፅም ማቆም የተቻላቸው አይመስልም። የኮሌራ በሽታ ከዚህ በላይ የከፋ ጥፋት ከማስከተሉ በፊት ለመከላከልና ወረርሽኙን ለመቀነስ በዓለም ዙሪያ ያሉ የጤና ኃላፊዎች ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ በፈረንሳይ ተሰባስበዋል። ጉዳዩን አስመልክቶ የአገራት የጤና ኃላፊዎች የዓለም የጤና ድርጅት በጎ አድራጊና ለጋሽ ድርጅቶች በጋራ ሲሰባሰቡ ይህ የመጀመሪያ እንደሆነ የቢቢሲ ዘገባ አስታውቋል።

በጉባዔው እስከ 2030 ድረስ ባለው አስራ ሁለት ዓመታት ውስጥ የኮሌራ ወረርሽኝ መጠንን ዘጠና በመቶ ለመቀነስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል። የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በሽታው በድህነት ውስጥ ያሉና ደካማ አገሮችን የሚያጠቃ እንደመሆኑ በጭራሽ ልንቀበለው የማይገባ መሆን አለበት ብለዋል።

የቀድሞ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማርጋሪን ቻን የኮሌራ በሽታን በመከላከል ረገድ በስልጣን በቆዩባቸው ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት የበሽታው መጠንና ስፋት እያደገ የመጣበት በመሆኑ ተገቢውን ትኩረት አልሰጡትም ተብለው ይወቀሳሉ።

በእርግጥም ባለፉት ጊዜያት በበሽታው የተጠቁትን ለመድረስና የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በተጋላጭ አካባቢዎች እንዲኖር ከሌሎች የተራድኦ ድርጅቶች ጭምር የሰሯቸውን ስራዎች ድርጅቱ ይገልፃል። ያም ሆኖ በሽታውን በማስቆም ረገድ ባለፉት ዓመታት በበሽታው ሳቢያ ህይወታቸው የሚያልፍ ዜጎች ቁጥር መጨመርና በተለይም የህፃናት ተጠቂነት መጨመር የተሰራው ስራ ስኬታማ እንዳልነበር አመላካች ነው።

አሁን በድርጅቱና ሌሎች የጤና ዘርፍ አካላት በፈረንሳይ በተካሄደው ጉባዔ ለጉዳዩ የተሰጠውን ትኩረት አመላካች ነው ያስብላል። በኮሌራ ምክንያት የሚከሰት እያንዳንዱን ሞት በቀላሉ መከላከል እንደሚቻል የገለፁት ዶክተር ቴዎድሮስ ወረርሽኙን ለማስቆም የተቀረፀው ፍኖተ ካርታ ወሳኝ እንደሆነና ከአሁን ጀምሮ ሊተገበር እንደሚገባ ተናግረዋል።

በአውሮፓና ሰሜን አሜሪካ አገራት ላለፉት በርካታ አስር ዓመታት ከኮሌራ ነፃ ሆነው መቆየት የቻሉት በንፅህና የንፁህ ውሃ አቅርቦት ላይ በቀረፁት ፖሊሲ እንደሆነ የጤና ድርጅቱ ይገልፃል። በአገራቱ አንድ ዜጋ በማንኛውም ጊዜ ንፁህ ውሃ ማግኘት ሰብዓዊ መብቱ እንደሆነ ይቆጠራል። አሁንም ድረስ ደህንነቱ የተጠበቀ ውሃ የማያገኙ ከሁለት ቢሊየን በላይ ዜጎች በዓለም ዙሪያ መኖራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በፍኖተ ካርታው የንፁህ ውሃ አቅርቦት ተደራሽነትን ለማስፋት ከታቀዱ ስራዎች በተጨማሪም የኮሌራ መከላከያ ክትባት ተደራሽ እንዲሆን ይሰራል ተብሏል። በአሁኑ ወቅት በስድስት የአሜሪካን ዶላር የሚገዛው የአንድ ሰው ክትባት በተከታታይ ሦስት ዓመታት ከበሽታው ለመከላከል ያስችላል። የዚህ ክትባት ተደራሽነት በተለይም በኮሌራ ምክንያት የሚከሰተውን የህፃናት ሞት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።

ፍኖተ ካርታውን ለመተግበር አገራት፤ ለጋሾችና ቴክኒካዊ አጋሮች በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። ይህ ከሆነ ጦርነትና ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በሽታው በተስፋፋባቸው እንደ የመን ያሉ አገራት ጭምር ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

እንደ ድርጅቱ መረጃ ከሆነ በዓመት ህንድ ውስጥ ስድስት መቶ ሰባ አምስት ሺ አንድ መቶ ሰማንያ ስምንት ሰዎች በኮሌራ በሽታ ይያዛሉ። ከነዚህም መካከል ከሃያ ሺ ሁለት መቶ በላይ የሚሆኑት እጣ ፋንታቸው ሞት ነው። በሃይቲ ሁለት መቶ አስራ አንድ ሺ የሚሆኑ ሰዎች በዓመት በበሽታው ሲጠቁ ከሁለት ሺ አምስት መቶ በላይ የሚሆኑት ህይወታቸው አልፏል። በናይጄሪያ ከሁለት መቶ ሃያ ሺ ሰዎች በላይ በዚሁ በሽታ ተጠቅተው ከስምንት ሺ በላይ የሚሆኑት ሞተዋል። በኢትዮጵያም ከሁለት መቶ ሰባ አምስት ሺ በላይ ሰዎች ተጠቅተው ከአስር ሺ በላይ የሚሆኑት ህይወታቸው እንደሚያልፍ መረጃው ያመለክታል።

በተጠቀሱት አገራት ወረርሽኙ ምን ያህል እንደተንሰራፋ ከመረጃዎቹ መረዳት ቢቻልም በየመን ያለው ቀውስ ግን ከነዚህም አገራት በእጅጉ የከፋ ነው። በእርስበርስ ጦርነት እየታመሰች የምትገኘው የመን በዓመት ሰባት መቶ ሰባ ያህል ዜጎቿ በኮሌራ ይጠቃሉ። አፋጣኝ እርዳታና ህክምናን በቀላሉ ማግኘት በተሳናቸውም በበሽታው ምክንያት ከሁለት ሺ በላይ ሰዎች ህይወታቸው ይቀጠፋል። ከነዚህ መካከል አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ህፃናት መሆናቸው ደግሞ ሁኔታውን አሰቃቂ ያደርገዋል።

አውሮፓና አሜሪካ ይህን በሽታ መቆጣጠር የቻሉት ከመቶ ሃምሳ ዓመታት በፊት እንደሆነ የቢቢሲ መረጃ ያመለክታል። የፈረንሳዩ ጉባዔም ድሃ በሆኑ አገራት ወረርሽኙን ለማጥፋት የሚደረግ ወሳኝ ምዕራፍ እንደሚሆን ታምኖበታል።

በዓለም ጤና ድርጅት የኮሌራ ፕሮግራም መሪ የሆኑት ዶክተር ዶሚኒክ ሊግሮስ በበኩላቸው «በበሽታው ይህን ያህል የተጋነነ ወረርሽኝ በየዓመቱ መመልከት አንፈልግም፤ ወረርሽኙን የማጥፊያው መሳሪያ በእጃችን ይገኛል፤ እንጠቀምበት፤ ንፁህ ውሃና ሳኒቴሽን ካለ በሽታውን በቀላሉ እንዳይስፋፋ ማድረግ እንችላለን» በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 

ቦጋለ አበበ

 

 

Published in ዓለም አቀፍ
Saturday, 07 October 2017 17:19

የጋን ውስጥ መብራቶች

 

«ሀሎ እንደምን ዋሉ

«ማን ልበል

ስሜን አስተዋውቄ ለምን እንደ ደወልኩ ማስረዳቴን ቀጠልኩ። ምላሽ የሚሰጡኝ ምሁር ከአንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ናቸው፤

«እባክህ በዚህ ጉዳይ ባልነካካ ደስ ይለኛል፤ ሌላ ሰው ብትጠይቅ ይሻላል»

«በጉዳዩ ላይ ነፃ ምሁራዊ አስተያየት እንዲሰጡኝ ነው»

«እኔ ይቅርብኝ ከመንግስት ጋር መጋጨት አልፈልግም»

ስልኩ ተዘጋ፤ ቢዘጋም ተስፋ አልቆርጥም፤ አሁን አሁንማ ይህን መሰሉን አስተያየት ማስተናገድ እየተለመደ መጥቷል። ምሁራንን መፈለግና ለቃለ ምልልስ ፍቃደኝነታቸውን ጠይቆ ማነጋገር የእለት ተእለት ስራዬ በመሆኑ ደግሜ ስልኩን አነሳሁ፤ ደወልኩ፤ ደጋግሜ ደወልኩ። ስራነዋ። ሌላ ምሁር አገኘሁ።

«ሄሎ ዶክተር»

/እራሴን እና ተቋሜን አስተዋውቄ ጉዳዩን በሚገባ አስረዳኋቸው።/ ምላሹም እንዲህ ነበር፤

«ኦኬ! በዚህ ጉዳይ በተደጋጋሚ ጥናት አድርጊያለሁ። ተቋማችሁ ጥናቱን መሰረት ያደረገ አስተያየት በምን መልኩ እንደሚጠይቅ አያውቅምሲሉ መልሰው እኔኑ ጠየቁኝ።

«አልገባኝም በምን መልኩ ነው የሚጠየቀውእኔም ደግሜ ጠየኩዋቸው?

/በውስጤ ግን ክፍያ ፈልገው ይሆን የሚል ግምት አለ/

«የነገርኩህ የገባህ ይመስለኛል» ሲሉ ቆጣ ያለ ምላሽ አስደመጡኝ።

«ከፈለክ ነገርኩህ» አሉኝና ከመቅፅበት ስልኩ ተዘጋ።

ለስራዬ ብዙ ጊዜ ለማዘጋጃቸው አርቲክሎች እና ትንታኔዎች የምሁራንን ሀሳብ በፅሁፎቼ ለማካተት በተለይ ጉዳዩ ምሁራዊ ቃና እንዲኖረው በመፈለግ፤ግድም ስለሆነ ፍለጋው በስልክ፥ በአካልም ነው። መቦዘን የለም። በእርግጥ ይሄ የብዙ ጋዜጠኞች የእለት ተእለት ስራ ነው። ይሁን እንጂ ከአንዳንድ ምሁራን እያጋጠሙ ያሉት ምላሾች ግን «ልኑርበት፥ መነካካት አልፈልግም፥ የሌላ ምሁር ስልክ ልስጥህ፥ እኔ ይቅርብኝ» የሚሉና ሌሎችም ተስፋ የቆረጠ፤ ፍርሀት የተሞላበት አስተያየቶች ናቸው። የአንዳንዱ ምሁር ፊቱም ምላሹም ያስፈራል። እነዚህ ባህሪዎች ብቻ አይደሉም፤ መረጃ ለማግኘት መልከ ብዙ አጋጣሚዎችንና ምላሾችን እያሳለፍን ነው። በዚህ ሂደት ግን ሁሉንም ምሁራን መንቀፍ አልፈልግም። ይሄ የሁሉም መገለጫም አይደለም። ስራ ቢይዛቸው፣ ስብሰባ ቢወጥራቸው የእራት ሰዓቴን እንኳን ለኢንተርቪው አውለዋለሁ። ደውልልኝ የሚሉ ምሁራን ሞልተዋል። በየትኛውም ጉዳይ ለአንድ ጋዜጠኛ ሀሳብና አስተያየት መስጠት በሚለየን የሚቆጠር ህዝብን ማስተማር ነው ብለው የሚያስቡም በርካቶች ናቸው። ታዲያ እነዚህ እምቢተኞች ህዝብን ማሳወቅና ማስተማር ሀጢያት መስሏቸው ይሆን?

ከላይ ያነሳሁት የተወሰኑ አጋጣሚዎቼን ቢሆንም በዚህ ሙያ የተሰማሩ የስራ አጋሮቼ ሁሉ የከፋ ገጠመኝ እንደሚኖራቸው እገምታለሁ። እዚህ ላይ ምሁር ፈልጌ ይህን የመሰለ ምላሽ ሲገጥመኝ እውነቱን ለመናገር «ምሁር» ማለት ምን ማለት ይሆን ስል ራሴን ለመጠየቅ ተገደድኩ።

ምሁር የሚለው ቃል በተለይ በአሁኑ ወቅት ከመደበኛ ትምህርት ማለትም ከምስክር ወረቀቶች እንደ ዲግሪ፣ማስትሬትና ዶክትሬት ጋር ማያያዝ ይታያል። ይህ ትክክል ቢሆንም ከዚህም ውጪ መደበኛ ትምህርትን የተከታተሉ በተለያየ የሙያ ዘርፍ የተመረቁትን ምሁር ብለን ልንጠራቸው እንደሚገባን እምነቴ ነው።

ዲግሪ የሌላቸው ነገር ግን በኑሮ ተሞክሮ በስራና በተግባራዊ እንቅስቃሴ ያዩትንና ያለፉበትን የህይወት ልምዳቸውን መሰረት በማድረግ ነገሮችን አሊያም ክስተቶችን ማገናዘብ፤ ያሉበትን ሁኔታ በደንብ መተንተን የሚችሉ፤የወደፊቱን ለመተንበይ ምንም የማያዳግታቸው ብልህና አርቆ አስተዋይ ሰዎች መደበኛ ትምህርት /ዲግሪ/ ባይኖራቸውም ምሁር ተብለው ሊጠሩ ይገባል፤ አዎ! ስሙ ይገባቸዋል ባይ ነኝ።

በአንፃሩ ደግሞ ዲግሪ፤ ኧረ ዶክትሬትም ኖሯቸው የሰለጠኑበትን የሙያ ዘርፍ በደንብ ማገናዘብ የማይችሉ አንዳንድ ሰዎች አልፎ አልፎ መታየታቸው አልቀረም። የወደፊቱን ማየት፣ መተንተንና ማገናዘብ የማይችሉ «የተማርን ነን» የሚሉ እንዳሉ መካድ የለበትም። የአንዳንድ ምሁራን ሀሳብ የማካፈል እንቢተኝነት ከዚህም የመነጨ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለኝ ።

እነዚህ ሰዎች ይቅርታ«ምሁራን» በፅሁፌ መግቢያ በስልክ ያጋጠሙኝን ጨምሮ የተማሩ የሚመስሉ ነገር ግን ብርሃናቸው ለሀገር ለወገን ያልተረፈ የጋን ውስጥ መብራቶች ሆነውብኛል። ለነዚህ ይሆን ዘንድ አንድ ሀሳብ ለማንሳት ተገደድኩ።

«ምሁር» የሚለውን ጠቅለል በማድረግ ቃሉ ከመደበኛ ትምህርት ወይም ከዲግሪ እና ዶክትሬት መኖር አለመኖር ጋር መያያዙ ስህተት ነው የሚል አቋም አለኝ። የተማሩትን በተግባር ለመተርጎም ብልህነት የሚጎድላቸው ማገናዘብ የማይችሉ ስላሉም ጭምር። ይህ ብቻ አይደለም፤አሁን አሁንማ የተማርከውን መተርጎም የግድ የጥናት ፅሁፍ በማቅረብ የሚገኝን ገንዘብ ብቻ በመቃረም ምሁርነትን ላልተገባ ትርጉምና ጥቅም የሚያውሉ አሉ። ገንዘብ አያግኙ ማለቴም አይደለም። ሁሉንም ነገር ከገንዘብ ጋር ያጣበቁ ስላሉ ብዬ ነው። ለአገራቸውና ለህዝባቸው ያላቸውን እውቀት ማካፈል ደግሞ የዜግነትም ግዴታ አለባቸው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ምሁር እንዲሆን ያደረገችው አገሩ ናት። ህዝቡ ነው። ይህን ያስተማረን ወገንን ማስተማርና ማሳወቅ ምኑ ላይ ነው ጥፋቱ። አንድን ሀሳብ መደገፍም ሆነ መቃወም ከምሁራን ይጠበቃል። ሆኖም ግን ምክንያታዊ መሆን ደግሞ ይገባል። በዚህ አካሄድ ቅር የሚሰኝ መንግስት፣ ፓርቲም ሆነ ህዝብ አይኖርም ባይ ነኝ። ይሁን እንጂ ለህዝብ ጥቅም ሲባል ብርሀናቸው ከጋን ውስጥ እስካልወጣ ድረስ የምሁራን ፋይዳው ምኑ ላይ ይሆን? ምላሹን ለግላችን እናድርገው። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ያልተማሩ ብልህና አርቆ አስተዋይ ሰዎች ግን ከእነ የጋን ውስጥ መብራቶች በላይ ምሁራን ናቸው።

ታሪክን መለስ ብለን ስንመለከት ከዛሬው የአንዳንድ ምሁራን ባህሪና ተግባር ጋር ተመሳስሎ ይሁን አንዳች ነገር ያለ ይመስላል። ከ1970ዎቹ በፊትም ሆነ በኋላ የምሁራን ሚና ይህንን ይመስል ነበር ብሎ ቁርጥ ያለ ምላሽ መስጠት አይቻልም፤ አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም የተወሰኑ ምሁራን በሙያ ዘርፎቻቸውና በተሰማሩበት የስራ መስክ ተወስነው ኑሯቸውን ለመግፋትና የራሳቸውን ህይወት ማሻሻልን እንደ ዋና ተግባር በመውሰድ ከሀገራዊና ከህዝባዊ ጉዳዮች ተገልለው «አይመለከተንም» ብለው የተቀመጡ ለመኖራቸው ቤት ይቁጠረው።

በየሙያ ዘርፋቸው ግን የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ይሰጣሉ። ከዚህ ውጭ የሀገር ህልውና ላይ ተመስርቶ ህዝብን በሚመለከቱ ጉዳዮች ውስጥ ተሳትፎ ለማድረግ ያለመፈለግ አዝማሚያ የሚያሳዩ ቁጥራቸው ብዙ ነው። ይህ ከደንታ ቢስነት የሚመነጭ እንደሚሆን እገምታለሁ። ምክንያቱም ነፃ አስተያየትና የመናገር መብት ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ ይህ ችግር ነው ብዬ አልወስድም። ነገር ግን ባለፉት ስርዓቶች ይደርስ በነበረው የሀሳብ ገደብ ወይም «እባብን ያየ በልጥ በረየ» አስተሳሰብ ራሳቸውን ያራቁ ለመኖራቸው ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል።

ይሄ በእርግጥ ሊሆን ይችላል ወይም ደግሞ አንዳንዱ ምሁራን ባለፉት ስርዓቶች ካሳለፉት ተሞክሮዎች በመነሳት ራሳቸውን ከአገራዊ ጉዳዮች ያገለሉ ይኖራሉ። አንዳንዶች ደግሞ የሀገር፤የህዝብ ጉዳይ ያገባናል፤ ይመለከተናል ብለው ድምፃቸውን የሚያሰሙ፤በተመቻቸው መንገድ አንዳንድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ምሁራን አሉ። በዚህም የተነሳ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ቢኖርም ለመቋቋም የሚሞክሩ፤ዝግጁ የሆኑ ምሁራን መኖራቸው መዘንጋት የለበትም።

ለህዝብና ለሀገር ወገንተኛነታቸውን ሳያሳዩ በስልጣን አዙሪት ዙሪያ ብቻ በእሺ ባይነት ወይም ደግሞ በአጎብዳጅነት የሚንቀሳቀሱ ምሁራን ለመኖራቸው አንዳንድ ተቋማት ራሳቸው ምስክር ናቸው። በተለይ አሁን ባለንበት የምሁራን ሚና ይህን አሊያም ያን የመሰለ መልክ ብቻ ነው የያዘው ብሎ ማጠቃለል እጅግ አስቸጋሪ ነው። እውነት በእኔ እድሜ መልከ ብዙ ምሁራንን ያየሁበት ጊዜ ቢኖር ይሄ የመጀመሪያዬ ነው።

ምሁራን ከላይ በመግቢያዬ ያነሳሁትን ባህሪ የሚያሳዩት ከፖለቲካው በመራቃቸው ይሆን? እንጃ !ብቻ በተወሰነ ደረጃ የራቁም ያልራቁም አሉ። እዚህ ላይ አንድ መታወስ ያለበት ጉዳይ አለ። አንድ ሰው የተማረና ያወቀ በመሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ የግድ መግባት የለበትም። ሁሉም ምሁር ፖለቲከኛ የሆነበት ሀገርና ህብረተሰብ የለም። ይህን ስል ማንም ሰው የፖለቲካ ዝንባሌ እንዳለው በማመን ነው። አንድን ነገር የመውደድ፥ የመጥላትና የመቃወም አዝማሚያ አለው። ሆኖም ግን ከፖለቲካ አስተሳሰብና ዝንባሌ ነፃ የሆነ ሰው የለም። የተወሰነው የምሁሩ ክፍል በስራ ባህሪው በሰለጠነበት የስልጠና አይነት ተወስኖ ይቀራል። ሁሉም የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርም ፖለቲከኛ አይሆንም።

በገዥው ፓርቲም፣በተቃዋሚም ውስጥ ምሁራን አሉ። በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ሀኪሞች የሆኑ ወይም የነበሩ በአመራርም በአባልነትም ይንቀሳቀሳሉ። ሁሉም ምሁር ግን በተደራጀ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ አይገባም።

ምንም ይሁን ምን አገር ሳይተርፋት አስተምራ በተለይ ደግሞ በሰለጠነበት ትምህርት፤ምርምር በሚያካሂድበት ዘርፍ ለሚጠየቀው ሙያዊ አስተያየት ንፉግ መሆን አይገባም። አንድ ምሁር ምሁር የሚባለው ወይም ደግሞ ከብርሀን ጋር የሚመሰለው የተማረበትን በተግባር ሲያሳይ ነው። ይህ የማይሆን ከሆነ በተለይ ደግሞ ያለውን እውቀት በምሁራዊ አንደበቱ ወይም አስተያየት ያለውን ለህዝብ በማሳየት ብርሀን መሆን መቻል በህይወት ተሞክሮም ይሁን በትምህርት ያገኘውን እወቀት ማካፈሉ እውነት የምሁሩ ስያሜውም ያስገድደዋል ባይ ነኝ።

አለበለዚያ ግን ብርሀን ብርሀንነቱ የሚታወቀው በጋን ውስጥ ታፍኖና ንፉግ ሆኖ ሳይሆን ያለምንም ገደብ ከጋን ውጭ በሚሰጠው ብርሀን ብቻ ነው። በመሆኑም በተለይ አንዳንድ ምሁራን የዚህ ፅሁፍ ዋና አላማም ለእነርሱ ነውና ከጋን ውስጥ መብራትነት ያለፈ ብርሀን መሆን አለባቸው መልዕክቴ ነው። ለዚህም ምንም ቅድመ ሁኔታ ማዘጋጀት አይገባቸውም። ይህ ሲሆን ለሁሉም ይጠቅማል፤ በተለይ ለአገራችን ይበጃል።

 

ሀብታሙ ስጦታው

 

Published in አጀንዳ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።