Items filtered by date: Sunday, 08 October 2017
Sunday, 08 October 2017 21:24

ድሮ… ቀረ!!?

ድሮንም ዘንድሮንም ያዩ ብዙዎች ድሮ ቀረ ይላሉ። ሁሉም ነገር መቼ ቀረ? ድሮ። ይሄ ድሮ የሚባል ጊዜ አሁን ላይ ሳይናፍቀን አልቀረም። ድሮ ኑሮ ሁሉ ጥሩ ነው፤ ባለቀለም ቴሌቪዥን ባይኖርም ቀና አመለካከት ያላቸው ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ብዙ መኪና ባይኖርም የእግር መንገድ የሚያካሂዱ ሞልተዋል። ድሮ ሰዎች ደግ ነበሩ።

ዋጋቸው አንድ ብር ያልደረሰ የምግብ ዓይነቶች ብዙ ነበሩ፤ ክትፎን ጨምሮ። ዛሬ ከአንዱ የአዲስ አበባ ጥግ ወደከተማዋ መካከል ላይ ለመድረስ የማይበቃው ሰላሳ ብር፤ ድሮ የባለሀብት ኪስ ውስጥ እንጂ ሌላ ማን ጋር ይገኛል? 18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች የሃምሳ ብር ኖታ ምን ይመስል እንደነበር ማወቃቸውንም እንጃ! ድሮ ኑሮ ርካሽ ነበር።

በቀለም አልባው ቴሌቪዥን ለመመልከት ሻል አለ የሚባል ቤት ልጆች ያቀናሉ፤ብቻ ምን አለፋችሁ የሁሉም ሰው(ከእኔ ጋር ንግግር ያደረጉትን ለማለት ነው)ከድሮ ቀረ ጋር ተያያዘብኝ። እናም ጥያቄን መጠየቅ ተያያዝኩት ስለ ፍቅር አባቶችን ብጠይቅ፡ ፍቅርማ በኛ ጊዜ ቀረ አሉኝ፣ እናቶችን ብጠይቅ፡ ፍቅር ከ ውሀው ምንጭና ከትልቁ ዋርካ ስር ድሮ ቀረ አሁንማ እንኳን ፍቅር ዋርካውም አይገኝ አሉኝ። የሀይማኖት አባቶችን ብጠይቅ ፡ አይ ልጄ በዚህ የሰይጣን ዘመን ፍቅር የታለ ብለህ ነው ፍቅር እኮ ድሮ ቀረ ሲሉ መለሱልኝ። የጦር መሪዎችስ ምን ይላሉ ብዬ ብጠይቅ የድሮ ፍቅር የወታደሮቻችንን ጉልበት የመበዝበዝ አቅም አለው አሉኝ፣ ወጣቶችንም ጠየቅኩ ፡ ፍቅር በፊልም እና በመፅሐፍ ላይ ቀረ አሉኝ፣ እንደውም ይባስ ብለው ፍቅር የገንዘብ ነው እውነተኛ ፍቅር የሚባል ነገር የለም፤ ሁሉንም ገንዘብ ያመጣዋል ብለውኝ እርፍ አሉ፡፡

ይህንን ሃሳብ እያሰላሰልኩ ሳለሁ አንድ ወዳጄ ያጫወተኝ ነገር ትዝ አለኝ ትዝታ ድሮ ቀረ እንዳትሉኝ ፤አንድ አዛውንት እየተጓዙ ሳለ ሁለት ልጆች ተጣልተው ሰዎች ሲገላግሉዋቸው ያያሉ፡፡ ከዛ ጉዳዩን ለማጣራት ጠጋ ብለው ከሰዎቹ መሀል አንዱን ልጅ "ምንድነው?" ሲሉ ይጠየቁታል። ልጁም "ልጆች ተጣልተው ነው"አዛውቱ ሰውዬም መልሰው "ተጎዳዱ" ልጁ መልሶ "አይ አንደኛው ልጅ በድንጋይ ተፈንክቷል" እሳቸውም "ደማ?" ልጁ "አይ እብጠት ብቻ ነው""ኤጭ ድንጋይስ ድሮ ቀረ! የድሮ ድንጋይ ቢሆን ሁለት ቦታ ተርክኮ ነበር የሚጥለው" ብለው ጉዞአቸውን ቀጠሉ… ድሮ ያለቀረ ነግረ ምንድነው እያልኩ ማሰላሰል ጀመርኩ። በመሀል አንድ በእድሜ ጠና ያሉ ሰው አገኘሁ እናም እያሰብኩት ስላለው ሃሳብ ማለቴ ስለ ድሮ ቀረ ጠየኳቸው ሁሉም ድሮ እንደቀረ ነግረውኝ አንድ ሃሳብ ጨመሩል፡፡

ውሽምነት እንኳ ድሮ ቀረ ከአንድ በላይ መሄድ በሃይማኖትም በባህላችን ነውር ቢሆንም የአያቶቻችን ጊዜ የነበረው ውሽምነት የሚያስቀና ነበረ አሉኝ፡፡ እንዴት? ብዬ ጠየኳቸው የውሽማ እንክብካቤ ባል ቀምሶት የማያውቀውን በቅቤ የተቅለጠለጠ ጭብጦ፣ ቋንጣ ፍርፍር፡ ገንፎ …..ይቀርብለት ነበረ ሲሉኝ ፤ ከዚህ በኋላ ማንንም አልጠይቅም ብዬ ለራሴ ቃል ገባሁ። ነገር ግን ሃሳቡ ከውስጤ ሳይወጣ እና ድሮ ያልቀረ ነገር እና በዛሬ ላይ እምነት ያለው ሰው ማነው የሚለውን ለማግኘት በሚፍጨረጨረው አዕምሮዬ እና ከማገኘው መልስ የተነሳ ጉዳዩን በመተው እና ባለመተው መሀል ሆኜ ከእራሴ ጋር ሙግት ገጠምኩ ፡፡

ይሄ የድሮ ቀረ አባዜ… አንዳንድ ጊዜ ትርጉም አያጣባችሁም? ለምሳሌ አንዱ አስፓልት ዳር መኪናውን አቁሞ ሻይ እየጠጣ… የፓርኪንግ ሰራተኛዋ ትመጣና ቲኬት መኪናው ላይ ታደርጋለች። ትንሽ ቆይታ እንደገና ትመጣለች… ብዙም አልቆየችም (ለሱ እንደመሰለው) ሌላ ሁለተኛ ቲኬት ትደርብበታለች ይሄን ጊዜ ሰውየው "እንዴ! ሰላሳ ደቂቃ ሞላው እንዴ?" ቢላት "የዘንድሮ ሰላሳ ደቂቃ ምን አላት ብለህ ነው" ብላው መሄድ " ጊዜ ድሮ ቀረ እቴ!" በሚል አይነት እውነትም ግን አስተውላችሁት ከሆነ ዘንድሮ እኮ ጊዜው እንደ ቦልት ነው የሚሮጠው፤ የግድግዳ አልያም የእጃችን ሰዓት ላይ ያለው የሰዓት ቆጣሪው ዘንግ የተሰበረበት ዘመን ላይ ያለን ነው የሚመስለው። ሰዓቱ በደቂቃ ፍጥነት ሆኗል የሚነጉደው፤ ከሁሉ ደግሞ ብሽቅ የሚያደርገው ጊዜውም ይሮጣል፣ እኛም እንሮጣለን ግን ጠብ የሚል ነገር አለመኖሩ ነው። በቃ አንዱንም ሳንይዘው ይመሻል ጊዜ ድሮ ቀረ እቴ!

የድሮ ጊዜ እንደ ፊውዳል መሪ ጅንን ብሎ፣ ጎርደድ… ጎርደድ… ይል ነበር አሉ፤ አሉ ነው የዘንድሮው ግን ልክ መድረኩን ለሌላዋ እንደምታስረክብ የፋሽን ሞዴል ነጠቅ… ነጠቅ እያለ ነው የሚነጉደው። ይሄ አሉ አይደለም፤ ነው! አይ ጊዜ… ጊዜ ድሮ ቀረ እቴ!ታዲያ ከተረጋጋሁ በኋላ ዙሪያ ገባዬን ማስተዋል ስጀምር አሁንም ተስፋ አለ ፤ቀንን እና ዘመንን ብሩህም ጨለማም የሚያደርገው በዘመኑ እና በቀኑ ላይ የሚኖረው ሰው ነው ፤ቀኑ በራሱ ደግም ክፉም ሊሆን አይችልም ፡፡ ድሮ ቀረ ባሉት ሰዎች ዘመን ያለው ተስፋ፣ ደስታ፣ ሰላም እርካታ ሁሉም ነገር አሁንም እንዳለ ተረዳው፡፡

 

መርድ ክፍሉ

Published in መዝናኛ

ህይወት ብዙ ውጣውረዶች የበዙባት ነገር ግን ለታገለና ለለፋ መልካም ነገሮችን የምታቀናጅ መሆኗን ብዙዎች ይናገራሉ። ለእዚህም ምስክር የሚሆኑት ደግሞ በዚህ አምዳችን የምናቀርባቸው እንግዶቻችን ናቸው። ለዛሬ «የህይወት እንዲህ ናት» አምዳችን ብዙ ውጣውረዶችን ያሳለፉ፤ ከዚያም የሚፈልጉትን ነገር ያገኙና ወደፊትም ገና እደርስበታለሁ ብለው የሚያስቡትን ነገር ለማሟላት በመትጋት ላይ የሚገኙ አንድ እንግዳ ይዘንላችሁ ቀርበናል።

እንግዳችን ከትንሽ ደረጃ ተነስተው ዛሬ ላይ ዋናውን የሼር ድርሻ በያዙባቸው ሁለት ኮሌጆች ከአንድ ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ፤ ለበርካቶችም የዕውቀት ብርሃንን ያዳረሱ ናቸው። ለብዙዎችም ተስፋ በመሆን ህይወታቸውን እየመሩ ይገኛሉ።

በተለይ በበጎ አድራጎት ሥራቸው ብዙዎች ያውቋቸዋል። «በእኔ የደረሰ በወገኔ ላይ ሊደርስ አይገባም፤ በዚህ ምድር የመጣሁትም ለዓላማ መሆኑም ይሄን መፈጸም ይኖርብኛል» የሚል አመለካከትን ሰንቀው የሚንቀሳቀሱም ናቸው። ታዲያ እኒህ ሰው ማን ይሆኑ ካላችሁ አቶ ሞገስ ግርማ ካሳ ይባላሉ። አቶ ሞገስ በርካታ የህይወት ተሞክሮዎችን አሏቸው። ለአንባቢያን ያስተምራሉ የምንላቸውን ብቻ መራርጠን እንዲህ አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ።

ውልደትና እድገት

እንግዳችን በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ አቧሬ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው ተወልደው ያደጉት። አቧሬ ብዙዎች ተፋቅረውና ተዋደው ይኖሩባታል፤ በየአቅጣጫው መንገድ ብቻ ያላት በመሆኗ ወደአካባቢው የገባ ሰው ለመውጣት ስለሚቸገር «ቤርሙዳ ትሬአንግል» ብለውም በቅጽል ስም እንደሚጠሯት ከእንግዳችን ጋር በነበረን ወግ ሰምተናል። እንግዳችንም በዚህ ስፍራ ከእናታቸው በልዩ መኮንን እና ከአባታቸው ግርማ ካሳ በ1965.ም ተወለዱ። ምንም እንኳን ቤተሰቦቻቸው ገቢያቸው አናሳ ቢሆንም የሁለተኛ ልጃቸው መወለድ እጅግ ደስተኛ አድርጓቸው እንደነበረ ወላጆቻቸው የነገሯቸውን ዋቢ በማድረግ ባለታሪኩ ያስታውሳሉ።

እንግዳችን በዚህ ሰፈር እንደማንኛውም ልጅ ዳዴ ብለው ያደጉ ሲሆን፤ የትምህርት እድሜያቸው እስኪደርስም ብይ በመጫወት፣ ቆርኪና አባሮሽ እንዲሁም ሌሎች ጨዋታዎችንም በመጫወት የልጅነት ጊዜያቸውን አሳልፈዋል፡፡ እንደልጅም ብዙ የሚያስቸግሩ አልነበሩም። ይልቁንም ገና ከልጅነታቸው ትንሹንም ትልቁንም በማስታረቅ ተግባር ላይ ይሳተፉ ነበር። እግር ኳስ ወዳድነታቸውና ሰዎችን በማክበር ችሎታቸው ብዙዎች «ህጻን አይደለም፤ ሲፈጠርም ትልቅ ሆኖ ነው የተወለደው» ይሏቸዋል። በእዚህም በሰፈሩ ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ልጆች መካከል አንዱ ነበሩ።

የትምህርት ህይወት

የዛኔ እንደዛሬው መዋዕለ ህጻናት ባለመኖሩ፤ አቶ ሞገስ የትምህርትን ጣዕምን ያወቁት በቄስ ትምህርት ነው። ግቢ ገብርኤል በመግባት እስከ ዳዊት ድረስ ተምረዋል። ከዚያ በድሮው ደጃች ይልማ በአሁኑ ደግሞ ቀበና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ተማሩ። ቀጥለውም ራስ ሙሉጌታ ወይም በዛሬው አጠራር ብርሃን ጉዞ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታተሉ። ከዚያም ከቤታቸው ትንሽ ራቅ በሚለው ባልደራስ ወይም ምስራቅ አጠቃላይ ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት ገብተው እስከ 12ኛ ክፍል ተማሩ። ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም።

የሚፈልጉትንም ማግኘት አይችሉም ነበር። ምክንያቱም እናታቸው የቤት እመቤት፤ አባታቸውም በግንባታው ዘርፍ የቀን ሰራተኛ ነበሩ፡፡ ስለዚህ የሚፈልጉትን ነገር ለማሟላት በራሳቸው ይጥሩ ነበር። ለምሳሌ መስከረም ሲጠባ በእንቁጣጣሽ በዓል ላይ አበባ እያዞሩ ይሸጡና ደብተርና እስክሪብቷቸውን ይችላሉ። የሚያገኙትን ባለማባከን፤ ቤተሰብን እንዲህ አድርጉ ብሎ ባለማስቸገርም ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡ ትኩረታቸው ትምህርታቸው ላይ ስለሆነም ሌሎች ተግባራትን እንዲያከናውኑ አይፈቀድላቸውም። በትምህርት ቤት ቆይታቸውም የ25 ሣንቲም ዳቦና ሻይ ምሳ በልተውም ይውሉ ነበር፡፡ ሲጠፋም ምሳ ሳይበሉ የሚውሉበት አጋጣሚም እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

በእርግጥ ሳይደግስ አይጣላ አይደል የሚባለው እንግዳችን የተቸራቸው ልዩ ስጦታ ነበራቸውና ምንም ሳይሰማቸው ችግርን እንደ ችግርነቱ ተቀብለው ወገባቸውን ታጥቀው ይማሩ ነበር። በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ እያለፉ ቀጣዩን የትምህርት ደረጃ ለመማር የበቁትም ይህ ችሎታ ስላላቸው ነው። እንግዳችን ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ የኬሚስትሪ ትምህርትን በጣም ይወዱት ነበር። እናም በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ሲገቡም የመጀመሪያ ምርጫቸው እርሱን አድርገዋል። ፔሬዲክ ቴብልን ያለምንም ችግር በቃላቸው ሸምድደው በመያዛቸው ተማሪዎቻቸው «ሞገስ ፔሬዲክቴብል» የሚል ቅጽል ስም እስኪያወጡላቸው ያደረሳቸውም ነበር። እናም በዚህ ዘርፍ በከፍተኛ ውጤት ተመርቀው ኮሌጁን ለቀዋል። በዚህ ሙያም ትንሽ ከሰሩ በኋላ ትምህርት በቃኝን አያውቁምና ሌላ የሙያ መስክ ለመማር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገቡ። በኮንፒውተር ሳይንስ ዲግሪያቸውንም ያዙ።

ይህ ጊዜ ለእርሳቸው እጅግ ፈታኝ ወቅት እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ሞገስ፤ የወቅቱ ምርጫን ተከትሎ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ግርግር የነበረ እንደመሆኑ አንዳንድ ወጣቶች ድንጋይ ይወረውሩ ነበር፡፡ እርሳቸው ግን በዚያ ፋንታም ቤተሰቦቻቸውን ሊያግዙ የሚችሉበን መንገድ ቀይሰው ከድንጋይ ውርወራ ይልቅ መጽሐፍ ጽፎ ለገበያ ማቅረብ ላይ አተኩረው ነበር።

እናም «ተማሪው ድንጋይ ሲወረውር እኔ መጽሐፍ እወረውር ነበር፤ ለእዚህ ያበቃኝ ደግሞ ብዙ ጊዜ አጠሪራዬን ተማሪዎች ይሻሙት ስለነበር ነው፤ ይህንን ከወደዱት መጽሐፍ ብጽፍ ምን ሊያደርጉት ይችላሉ የሚል ስሜት አደረብኝና በነበረኝ ጊዜ ጻፍኩ። ማተሚያ ቤቶችም በሦስት ብር አተሙልኝ። ከዚያ በወቅቱ በነበረው ግርግር ውስጥ ሆኜ በ9 ብር መጽሐፉን ሸጥኩት፤ ትርፋማም ሆንኩበትና ቤተሰቤን ከችግር ለመታደግ በቃሁ» ሲሉ አውግተውናል።

አቶ ሞገስ፣ ከአልፋ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት ሌላ ዲግሪ ያገኙ ሲሆን፤ የህንድ አገር የሚገኘው ሲኪ ማኑፓል ዩኒቨርሲቲ ወኪል ከሆነው ስሪ ሳይ ኮሌጅ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሊይዙ ችለዋል።

የሥራ ጅማሮ

አቶ ሞገስ ምንም እንኳን ተማሪ ሆነው በትርፍ ጊዜ ሰራተኝነት በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ቢያገለግሉም በቋሚነት ግን ሥራን «» ብለው የጀመሩት ሰበታ አካባቢ በሚገኘው ጌቴሰማኒ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የኬሚስትሪ መምህር በመሆን ነው። ከዚያ ወደ መርካቶ አቅንተው ራጉኤል ትምህርት ቤት ለተወሰኑ ዓመታት አስተማሩ። ቀጥለው ደግሞ ኮከበ ጽባሕ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገቡና ማስተማር ጀመሩ። ከተወሰኑ ዓመታት ቆይታ በኋላ የኮንፒውተር ሳይንስ ትምህርታቸውን ስላጠናቀቁ ደራርቱ ቱሉ ትምህርት ቤት በመግባት ኮምፒውተር ሳይንስ ያስተምሩ ጀመር።

በዚህ መልኩ ሲሰሩ ከቆዩ በኋላም በቢሾፍቱ በሚገኘው የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒዩተር ሳይንስና ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍልን በመምህርነት ተቀላቀሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲው ከማስተማር ጎን ለጎንም ሌላ የህይወት መስመራቸውን ጀምረዋል፡፡ በዚህም ጌጅ እና ኪዊንስ ኮሌጆችን ጨምሮ በትርፍ ጊዜያቸው ይሰሩ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ስለ ኮሌጆቹ አጠቃላይ ሂደት እንዲያውቁ አስችሏቸዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በመጀመሪያ ጌጅ የሚባለው ኮሌጅ የእርስ በእርስ አለመግባባት ስለተፈጠረ እንዲሸጥ ተወሰነበት። እናም ኮሌጁን ለመግዛት አስር ሰዎች ተደራጅተው መጡ።

በወቅቱ እርሳቸው ምንም እንኳን ገንዘብ ባይኖራቸውም ጥቂት የቆጠቧትን በብድር አዳብረው ከሼሩ ውስጥ መካተት እንደሚፈልጉ ጥያቄ አቀረቡ። ይሁን እንጂ ለጊዜው ተቀባይነትን አላገኙም ነበር። ቆይቶ ግን አባላቱ እርሳቸው እንደሚያስ ፈልጓቸው ተረዱና አስገቧቸው። በዓመቱም ኮሌጁ እንዲሸጥ በመወሰኑ ዛሬ ላይ አንበሳውን ድርሻ ይዘው እንዲሰሩ አግዟ ቸዋል። ከመምህርነቱ ባሻገርም የቢዝነስ ሰው እንዲሆኑም ረድቷቸዋል። በኪዊንስ ኮሌጅም ቢሆን ይኸው ነው የሆነው። ትንሽ ለየት የሚያደርገው ለትምህርት ቤቱ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ስለሚሰሩ ባለቤቱ ከብዶት ሊሸጠው ሲል እርሳቸው እንዲገዙት መጋበ ዛቸው ነው። እናም የሁለቱ ኮሌጆች ከፍተኛ ባለድርሻ ለመሆን በቁ፡፡ እርሳቸው ግን ዛሬም ኮሌጆቹ የእኔ ሳይሆኑ የተማሪዎቹ ናቸው ነው የሚሉት፡፡

መምህርነትና ቢዝነስ

«መምህር መሆንን ብዙዎች አይወዱትም፤ ገንዘብ የለውም ልፋት ብቻ ነውም ይሉታል። ይህ ግን በእኔ እይታ ትክክል አይደለም። እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ የምወደውና የምመኘው ሙያ ነው። እናም ይህ ሙያዬ ዛሬ ላይ ለትልቅ ቁም ነገር እንድበቃ አድርጎኛል፤ እናም አንድ አስተማሪ ስራውን እየሰራ ሌሎች የቢዝነስ አማራጮችን የሚጠቀም ከሆነ ይህንን ሙያ የማይወድበት ምክንያትም የለም» የሚሉት እንግዳችን፤ ጥሩ መምህር በመሆን ሙያን ወድዶ እስከመጨረሻው ለመጓዝና የፈለገውን ለማግኘት የሚቻልበት መንገድ ነው ይላሉ፡፡ በተጨማሪም የቢዝነስ ሰው መሆንንም ማግኘት የሚቻለው ብዙ በማወቅ ነውና ይህ ደግሞ ዋና መነሻ እንደሚሆን ይገልጻሉ።

ይህንን ያሉት ደግሞ ያለምክንያት አይደለም። የእርሳቸውን ተሞክሮ አብነት አድርገው ነው። ዲፕሎማ እያሉ እውቀቱና ብቃቱ ስለነበራቸው የመማሪያ መጽሐፍ ጽፈው የገቢ ምንጫቸውን ማሳደግ እንዲችሉ ያደረጋቸው መምህር በመሆናቸው ነው፡፡ ከዚያ ውጪም መምህር በመሆናቸው የሰዎችን ስሜትና እምነት በማግኘት የኮሌጅ ከፍተኛ ባለድርሻ ሆነውበታል። እናም መምህር መሆን በቅርበት ሰዎችን በቀላሉ የመረዳት ክህሎትን ያቀዳጃልና ከሌሎች ሙያዎች በበለጠ የቢዝነስ ሰው ለመሆን መተኪያ የሌለው ሙያ ነው።

ፈታኝ ጊዜ

እንግዳችን በህይወታቸው ብዙ ፈተናዎችን አሳልፈዋል፤ ይሁን እንጂ ሁለቱ ነገሮችን እንደ ትልቅ ፈተናዎች ያነሳሉ። ከነዚ ህም መካከል አንዱ በልጅነት ህይወታቸው ውስጥ ያሳለፉት የችግር ውጣውረድ ሲሆን፤ በዚህ መስመር ውስጥ እያሉ የአባታቸው እንስፍስፍነትና የቤተሰቡን ስቃይ እጅግ ያሳስባቸው ስለነበር ከቁርስ አንስቶ እስከ እራት ድረስ ምንም ሳይበሉ በላራይ ብረሪ ሲያጠኑ የሚቆዩበት ጊዜ ነው። በተለይም ደግሞ የሚሰቀቁት ቤት ውስጥ ምግብ ሳይኖር የቤተሰቡ አለመግባባትና መጨቃጨቅ በጣም ይዘገንናቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።

አባታቸው ጠዋት ላይ መዶሻና አካፋ እንዲሁም ሌሎች መሳሪያዎችን ይዘው ሥራ እሰራለሁ ብለው ወጥተው ማታ ግን ምንም ሥራ ሳይሰሩ ከተመለሱ የቋጠሯትን ምግብ እንኳን ሳይቀምሱ ነበር የሚመለሱት። ምክንያቱም ከሰራሁ ለቤተሰቦቼ ምግብ መግዢያ የሚሆን ገንዘብ ይዤ እገባለሁ ካልሰራሁ ግን ምን ይበላሉ ብለው ስለሚያምኑ ነው። እናም የቋጠሯትን ምግብ ልጆቹ እንዲመገቡ ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ ለህጻኑ እንግዳችን ጭንቀትና ከአዕምሮ በላይ ሸክም ይሆንባቸው ነበር። እናም ይህንን ሲያስታውሱት «ምን አለ የሁሉም ሰው አባት እንደእኔ አባት ሩህሩህ ቢሆን፤ በዚያው ልክ ይህ ስቃይ ማለፉ ለእኔ ትልቅ ተስፋ ሆኖኛል»ይላሉም።

ሌላው ፈተናቸው ደግሞ ዛሬ ላይ በስራ አካባቢ የሚያጋጥማቸው ችግር ሲሆን፤ በተለይ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዙሪያ ያለው ብልሹ አሰራር ሥራቸው ላይ ጫና እያሳረፈባቸው መሆኑ ነው። «አንድ ተቋም ለሥራ ጉዳይ ሄጄ ሳለ ምንም እንኳን የሚያስፈልጉትን ነገሮች ያሟላሁ ቢሆንም የሚሰጠኝ ምላሽ ግልጽነት የሌለውና ግላዊነት የተንጸባረቀበት ነው። በተለይም በአንዳንድ ሰራተኞች ላይ የሚታየው የአመለካከት ችግር ምን እንደሚፈልጉ እንኳን ለማወቅ ይከብዳል፤ በዚህ ምክንያትም ጉዳዩ እንደግለሰቡ አተያይ ይወሰንና በደቂቃ የሚያልቀው ሥራ ስድስት ወርና ከዚያ በላይ እንዲፈጅ ይደረጋል። ይህ ደግሞ በተለይ ቢዝነሱ ላይ ለሚሰራ አካል እጅግ ፈታኝ ነው» ይላሉ።

እንግዳችን፣ ምንም እንኳን ከዚህ በላይ ችግሮችን አሳልፈው የቆዩ ቢሆንም፤ በጥቂት ሰራተኞች የሚስተዋል በራስ ፍላጎት መጓዝ ሥራቸውን በአግባቡ አከናውነው ለአገር አገልግሎት እንዳያውሉት እንቅፋት እየሆናቸው መምጣቱንና የሚመለከተው አካልም በዚህ ዙሪያ ሰፊ ሥራ ቢሰራ መልካም መሆኑን አበክረው ይናገራሉ።

መዝናኛና ገጠመኝ

ገጠመኛቸው እንዲህ በቀላሉ የሚተረክና የሚነገር ብቻ አይደለም። ምክንያቱም ኖረውታላ፤ ይሁን እንጂ እስካሁን አይረሳኝም ብለው የነገሩንን አንድ ገጠመኝ ብቻ አንስተን እናውጋችሁ። ነገሩ እንዲህ ነው። ገና ከልጅነታቸው የሰንበት ትምህርት ቤትን ያውቁታል፤ ይሁንና ብዙም ብስለቱና እውቀቱ አልነበራቸውም፡፡ በዚህ ወቅት ላይ ሰንበት ትምህርት ቤቱ ይገለገልበት የነበረው አዳራሽ ግድግዳው ሲበዛ ወፍራም ነበር፡፡ እናም ወደዛ አዳራሽ ሲገቡ ስለውፍረቱ ምስጢር ያስቡ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በዚህ ስሜት ውስጥ እንዳሉ፤ ከመድረኩ አንድ መዝሙር ይቀርባል፡፡

መዝሙሩም «የሰማይ ቤታችን አማኑኤል የሰራው፤ ግንቡ ንጹህ ውሃ መሰረቱ ደም ነው» የሚል ሲሆን፤ በዚህን ጊዜ እርሳቸው የግድግዳው መወፈር ውሃ ስለሆነ ይሆናል የሚል ግምት ያድርባቸዋል፡፡ ይሁንና ንጹህ ውሃ እንዴት ሊሆን ቻለ፤ መሰረት የተባለው ደግሞ መሬቱ ነው እናም ምንም ደም የለም በማለት እግራቸውን እያሽከረከሩ መመልከቱን ቀጠሉ። ግን ምንም አይነት ደም መሬቱ ላይ የለም፤ ከዚያ ውሃ የሆነው ግንቡ ሊሆን ይችላል በሚል እየተንፏቀቁና ሌሎች እንዳያዩዋቸው እያረጋገጡ ግድግዳውን ተጠጉትና በእጃቸው ዳሰሱት። ነገር ግን ግንቡም ውሃ አይደለም። የመዝሙሩ ይዘት የሕጻንነት አዕምሯቸው ስላልተቀበለላቸውም ይሄንን ለማረጋገጥም የጉባኤው አስተባባሪ የነበረውን ሰው መጠየቃቸውና ምላሹን ማግኘታቸው የማይረሳ ትዝታቸው እንደነበር እንባ በተቀላቀለበት ሳቅ ፍንክንክ እያሉ አጫውተውናል።

ወደሚያዝናናቸው ነገር ስንገባ ደግሞ ብዙን ጊዜ ከራሳቸው ጋር ማውራትና መጽሐፍ ማንበብ እንዲሁም ገጣሚ ናቸው ባያስብላቸውም ካነበቧቸው ነገሮች በመነሳት ግጥም መጻፍ ይማርካቸዋል። በተመሳሳይ ደግሞ በተለይ እለተ ሰንበትን ከጓደኞቻቸው ጋር ተገናኝቶ መጫወትና የቢዝነስ ዘዴዎችን መቀየስ ወይም ደግሞ የተቸገሩ ሰዎችን ማገዝ ያስደስታቸዋል።

የአባት እውቀት ለልጅ ሲተርፍ

«አባቴ ለእኔ ትምህርት ቤቴ ነው፤ ችግርን እንዴት ማሳለፍ እንዳለብኝ አስተምሮኛል። ሳይሰራ መብላትም ጉዳት እንዳለው አሳውቆኛል» የሚሉት አቶ ሞገስ፤ ዕንባ በተቀላቀለበት ስሜት የአባታቸው የዋህነት እርሳቸውም ለድሆች አለኝታ፤ ለተቸገሩ መጽናኛ መሆንን እንዲለምዱ እንዳደረጋቸው አውግተውናል። ችግረኛ ሆኖ ማደግ ደግሞ ለብዙዎች ብዙ አስተምሮት እንዳለውም የተረዱት ልጅ እያሉ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ምክንያቱም አባታቸው «ችግረኛም ሆንክ ሀብታም ካንተ በታች ያሉትን መመልከት ከቀጣይ እድሜህ የበለጠ ነገር ያቀዳጅሃል። ስለሆነም ሁል ጊዜ በጎ አድራጊና ለጋስ ሁን» ይሏቸው ነበር። ታዲያ እርሳቸውም ይህንን የአባታቸውን ምክር በመቀበል ዛሬ ድረስ እጃቸውን እንዲዘረጉላቸው ለጠየቁ ሁሉ ያደርጋሉ።

በተለይም በልማት ስራዎች እገዛ ማድረግ በጣም ያስደስታቸዋል። ለምሳሌ መናፈሻዎችን መስራት፣ ለትምህርት ቤቶችም ሆኑ ሌሎች ተቋማት ቁሳቁስ መስጠት፣ የልማት ሥራዎችን ለሚያከናውኑ የልማት ድርጅቶች የተለያዩ እገዛዎችን ማድረግ ቋሚ ስራቸው አድርገው ይንቀሳቀሳሉ። በእርግጥ እስካሁን መዝግቤ አልያዝኩም ለጠየቀ ሁሉ መስጠትን ብቻ ነው ገንዘብ ያደረኩት የሚሉት እንግዳችን፤ አባታቸው የመከሯቸውን እያንዳንዳቸው ተግባራት እንደሚከው ኑትና ይህ ደግሞ ለውጥ እንደሚያመጣላቸው ያምናሉ። በእስካሁን ሂደታቸውም ከ500 ለሚበልጡ ተማሪዎች የትምህርት ወጪያቸውን ሙሉ ለሙሉ በመሸፈን እያገዟቸው፤ ከዚህ ለሚልቁትም በግማሽ ክፍያ የእውቀት ባለቤት እንዲሆኑና ራሳቸውን እንዲችሉ አድርገዋል፡፡ በዚህ ዓመትም እስካሁን አሳማኝ ችግር ያለባቸውን 25 ተማሪዎች በምርጫቸው ገብተው እንዲማሩ ፈቅደዋል።

ቤተሰባዊ ህይወት

አቶ ሞገስ የሦስት ልጆች አባት ሲሆኑ፤ ቤተሰቡን በመምራትና በማገዝ ደስተኛ ህይወትን እየመሩ የሚገኙ ናቸው። ልጆቻቸው ሁሉም በመማር ላይ ሲሆኑ፤ ከእነርሱ በተጨማሪ ያልወለዷቸውንና በተለያየ ችግር ውስጥ ሆነው በአጋጣሚ ያገኟቸውን ሌሎች ልጆች እያገዙ ይገኛል፡፡ እንግዳችን ያ የጥንቱ የቤተሰባቸው ህይወት ተለውጦ ዛሬ ላይ ደስተኛ መሆን መቻላቸው እጅግ ያረካቸዋል። አባታቸውንም ተንከባክበው በፊት ለመሸከም እንኳን ፈቃድ የማያገኙበትን የአናጺነት ወይም የግንበኝነት ተግባር እንደ ፎርማን (ተቆጣጣሪ) ሆነው በሚሰሯቸው ተግባራት ላይ አሰማርተዋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ዛሬ ላይ በህይወት ባይኖሩም ደስተኛ ሆነው ስላረፉ ግን እንዳልከፋቸውም አውግተውናል።

ወደ ፊት

«እስከዛሬ በተሰጠኝ ልክ እየሰራሁ ነው ብዬ አላምንም፤ እየተፍጨረጨርኩ ነው እንጂ፤ አገሬ ለእኔ ቤተሰቦቼ ለእኔ እንዲሁም ጓደኞቼ ለእኔ ብዙ ነገር አድርገውልኛል። ይሁንና እነርሱ የሰጡኝን ያህል አልሰራሁም። እናም በቀጣይ ብዙ መስራት የምፈልጋቸው ተግባራት አሉኝ» የሚሉት እንግዳችን፤ በቀጣይ የበጎ አድራጎት ድርጅት የመክፈትና ብዙዎችን በታቀደ መልኩ ማገዝ እንደሚፈልጉ፤ አሁን ላይ ብዙዎች ትምህርት ቤቶች ከማህበረሰቡ በዝብዞ መክበርን ብቻ ስለሚሹ በተለይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ሰፊ ሥራ መስራትን እንዳሰቡ አውግተውናል።

ማህበረሰቡ ለእያንዳንዱ ሰው የሆነ ነገር አድርጓል፤ ለእርሱ መለወጥም ትልቅ ሚናን ተጫውቷል፤ ይሁን እንጂ ዛሬ ላይ ያለነው ኢንቨስተሮች ይህንን እየተመለከትነው አይደለም። እናም ለዚህ ውለታው የምንከፍለውን ስንቅ ማዘጋጀት ይኖርብናልና እኔም ለተሰጠኝ ለመክፈል በየዘርፉ እየተሰማራሁ የምሰራ ይሆናልም ብለውናል።

የአንድ ስራ ቀጣይነት የሚረጋገጠው በራስ ቦታ ላይ ሲከናወን እንደመሆኑ፤ እስካሁን የነበሩበትን የኪራይ ቤት ስራ ለማቃለል ሲባል ለማስተማሪያና አስተዳደር ስራዎች የሚውል ባለ ዘጠኝ ፎቅ ሕንጻ ፒያሳ አካባቢ እያስገነቡ መሆኑን ገልጸውልናል፡፡ ይህም ላሰቡት ሥራ ውጤታማነት አጋዥ መሆኑን ያምኑበታል፡፡

ባለታሪኩ አቶ ሞገስ ያው ከላይ እንዳልነው ብዙ የሚነገሩ ቁም ነገሮች ያሏቸው ናቸው። ይሁን እንጂ አምዳችን ገድቦናልና ይህንን ያህል ካልን ይብቃን። ሰላም!

 

ጽጌረዳ ጫንያለው

 

 

 

 

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

 

አሜሪካ በአፍጋኒስታን ላይ ጥቃት የከፈተችበትን 16ኛ ዓመት ከአንድ ሳምንት በፊት ማክበሯ ይታወቃል፡፡ አሜሪካ ወደ አፍጋኒስታን ጦሯን ያዘመተችው እአአ በ2001 ሲሆን፤ ምክንያቱም መስከረም 11 በአሜሪካ የተፈጸመው የሽብር ጥቃት መሆኑ መዛግብት ይጠቅሳሉ፡፡

ግሎባል ሪሰርች ድረገጽ ያወጣው ዘገባ እንደሚያመላክተው፤ እአአ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ አልቃይዳ ለምዕራባውያን በተለይ ለአሜሪካ ፈታኝ ቡድን እየሆነ መጥቶ ነበር። እአአ በ1998 በኬንያ ናይሮቢ የአሜሪካ ኤምባሲ ግቢ እንዲሁም በታንዛኒያ ዳሬሰላም ቦምብ ማፈንዳቱን ተከትሎ በወቅቱ የቢል ክሊንተን አስተዳደር በአፍጋኒስታንና ሱዳን ሪፐብሊክ የኦሳማን ቢን ላደን መሸሸጊያ ናቸው በሚል ድብደባ ፈጽሟል፡፡

በጦርነቱ ጊዜ የበርካታ ሰዎች ህይወት የጠፋ ሲሆን፤ እአአ በ2015 ዋሽንግተን ፖስት ይፋ ባደረገው ሪፖርት ላይ እአአ ከ2001 እስከ 2014 በአፍጋኒስታን 149 ሺ ሰዎች ሞተዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የአሜሪካ ጦር አባሎች፣ ስራ ተቋራጮችና የተቃዋሚ ታጣቂዎች እንደሚገኙበት ጠቅሷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ 26 ሺ የሚደርሱ ንጹሐን ዜጎች በአፍጋኒስታን ህይወታቸውን በጦርነቱ ምክንያት አጥተዋል፡፡

የሞቱት ሲቪሎች ቁጥራቸው ሊጨምር እንደሚችል በመገመት በሰው አልባ አውሮፕላን ድብደባና በእግረኛም ጭምር የሚደረገው ጥቃት በቡሽ፣ ኦባማና ትራምፕ አስተዳደርም ቀጥሏል፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በቅርቡ በቀጣናው 4ሺ የፔንታጎን ወታደሮች እንደሚያሰማሩ አስታውቀው ነበር፡፡

 

በሪሁን ፍትዊ

Published in ዓለም አቀፍ

 

ውይይት። የእዚህን ቃል ቀጥተኛ ትርጉም ፍለጋ አንዳንድ የአማርኛ መዝገበ ቃላትን አገላበጥን። በኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ውይይትን «የኀዘን ንግግር፤ የለቅሶ ጭውውት» ሲል ይፈታዋል። በዚህ መሰረት መወያየት- መተዛዘን፣ መለቃቀስ፤ መወያያ- መተዛዘኛ የለቅሶ ቤት። ይህም «ዋየ» የሚለውን ቃል መሰረት ያደረገ ነው። ትርጉሙም ዋይ አለ፤ ዐዘነ፤ ተከዘ፣ ቆዘመ፤ አለቀሰ፣ ተወዛወዘ፣ አነባ ማለት ነው። ይህ ቃል ተዋየ፣ ተወያየ፣ ውይይት እያለ የሚቀጥል ነው።

በሌላ በኩል በ1993.ም ለህትመት የበቃው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ ውይይት የሚለውን ቃል እንደሚከተለው ይፈታዋል። ውይይት፡- 1. የሀሳብ ልውውጥ፣ ምክክር፣ ጭውውት። 2. ከሾፌር በስተኋላ አምስት አምስት ተሳፋሪዎችን የሚያስቀምጡ ሁለት ግራና የቀኝ አግዳሚ መቀመጫዎች ያሉት የከተማ ታክሲ። እንግዲህ እኛም የቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል መዝገበ ቃላት ላይ ባለው «ውይይት» ነው ዛሬ ላይ የምንግባባው። እንደው ነገሩን እንደመግቢያ ለጠቅላላ መረጃ አነሳነው እንጂ ጉዳያችንስ ወዲህ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በብዛት የመጽሐፍት ላይ ውይይቶች ተዘጋጅተው ታዳሚዎች ሲጋበዙ እንሰማለን። በዚህ በኪነጥበብና ባህል ገጽም ላይ እንዲህ ያሉ በርካታ ጥሪዎች ይቀርባሉ።

«ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል» የሚል መልዕክትም በተለያዩ ጊዜ፤ በተለይ መጻሐፍትን በሚመለከት ርዕሰ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ጎልቶ ይሰማል። የተደረጉ የመጻሕፍት ውይይቶችም በትዕይንተ መስኮቶቻችን ለማየትና ለመከታተል ዕድሉ ሰፊ ሆኗል። ታዲያ ከእነዚህ የመጽሐፍት ውይይት መድረኮች ምን ይገኛል? ምንስ ገጽታ አላቸው? የሚጎድል ነገርስ አለ ወይ? ይህንን በሚመለከት አነስ ያለች የጨዋ እይታ ላቀርብላችሁ እነሆ ጀመርኩ፥

የመጽሐፍት ላይ ውይይት ዛሬ የተጀመረ ነገር እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በጋራ ስለሚያውቁት ነገር ተሰብስቦ በጋራ የመነጋገር ነገር የአገራችን ባህልም ነው። ታዲያ ይህ የመጽሐፍት ላይ ውይይት መደበኛ /Formal/ በሆነ መንገድ የጀመረው ከ15 ዓመታት ወዲያ ነው። በዚህም ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ፈር ቀዳጅ በመሆን ስሙ ደጋግሞ ይነሳል። ይህም ቢሆን ግን ደራስያን፣ ገጣሚያን፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተሰባስበው ስለሥራዎቻቸው ሳይናገሩ ቀርተው አይደለም። እንዳልነው በመደበኛ ደረጃ፤ አንባቢን አሳታፊ የሆነን መድረክ ስናነሳ ነው የተጀመረበትን ዓመት ወዲህ ያቀረብነው።

በመጻሕፍት ውይይት መድረክ ላይ ታዳሚ ወይም ተሳታፊ ሰው ምን ያገኛል? የሚለው ጥያቄ አንድ ግለሰብ ብቻ በሚሰጠው መልስ የሚቋጭ አይደለም። ሁሉም እንደደረጃው፣ እንደእውቀቱ መጠን በቻለው ልክ ይጠቀማል፣ ይወስዳል። ነገር ግን ሁሉንም ሊያግባባ የሚችል አንድ ነጥብ አለ፤ እነዚህ የመጻሕፍት ውይይት መድረኮች የንባብ ባህልን ማዳበር የሚያስችሉ ናቸው። እንዴት ማለት ጥሩ፤ ያነበበው ከንባቡ ላይ የሚጠቅመውን ከራሱ ጋር እንዲያስቀርና ለሌላ ንባብ እንዲተጋ፤ ያላነበበ ደግሞ መጽሐፉን ማንበብ እንዲችል ብርሃን የሚያስገባ መስኮት የሚከፍት በመሆኑ ነው።

አንድ መጽሐፍ የተጻፈበት መቼት፣ የታሪክ ግንባታው፣ የተነሱ ሃሳቦች፤ ስለተጻፈበት ዘውግ ባህርያት ላይ ውይይት ይነሳል። ለምሳሌ አንድ የግጥም መጽሐፍ ለውይይት የቀረበ እንደሆነ መነሻ ሃሳብ አቅራቢው ባለሙያ «ግጥም ምንድን ነውከሚለው ጥያቄ በመጀመር ሰፊ ማብራሪያ ሊሰጥ ይችላል። በዚህም ከትምህርት ተቋማት ብቻ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀውን እውቀት ውስን ክፍል ታዳሚው ማግኘት ይችላል ማለት ነው።

ታዲያ በእነዚህ መድረኮች መጽሐፍት ብቻ ሳይሆኑ ሃሳቦችም ለውይይት ይቀርባሉ። ለውይይት ከሚቀርብ መጽሐፍ ወይም ሀሳብ በተጓዳኝ ለውይይት መነሻ ሃሳብ የሚያቀርቡ ባለሙያዎች እንዲጋበዙ ይደረጋል። ከእነዚህ ባለሙያዎችና ምሁራን የሚገኘው መረጃ ቀላል የሚባል አይደለም። ነገር ሁሉ በሃሳብ ይጀምራልና ለትውልድ የተሻለውን ሃሳብ ለማቀበልና አስተሳሰቡንም በበጎ ወገን ለመቅረጽ አንደኛ ሊባል የሚገባ መድረክ ነው ባይ ነኝ።

ይህን ሁሉ ያነሳነው ታዲያ ከታዳሚው አንጻር ነው'ንጂ መጽሐፉ ለሃሳብ ልውውጥ ከሚቀርብለት ጸሐፊ አንጻር አይደለም። ምንም እንኳን አንድ ጽሑፍ ወይም ድርሰት ከጸሐፊው እጅ ከወጣ በኋላ ደራሲው በዛ ሥራ ላይ ምንም ስልጣን የለውም ቢባልም፤ ለተሻለ ሥራ እንዲሁም ለእርማት ይሆነው ዘንድ ደራሲው ከዚህ መድረክ ተጠቃሚ ይሆናል።

«ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስ አበባ» የተሰኘውን መጽሐፍ ያበረከቱልን ዶክተር ሽብሩ ተድላ በትራኮን ህንጻ ላይ ይኸው መጽሐፋቸው ለውይይት ቀርቦ ነበር። ከውይይቱ ማብቂያ ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ የሚከተለውን አሉ፥ «ጸሐፍያንም በእንዲህ ያለ መድረክ ብዙ የመሳተፍ እድል ቢገጥማቸው ጥሩ ነው። መጽሐፍ በሚጽፉበት ጊዜ ሰዎች ይንቁብናል፣ አስተያየት ይሰጡብናል ከሚል ስጋት አይቀርቡም። አንድ ሰው በሥራው ከተማመነ ለሚነሳው አስተያየት መልስ ያገኝለታል። ደራስያን እንዲበዙ ያደርጋሉና እንዲህ ያሉ መድረኮች እንዲበራከቱ እመኛለሁ።»

በአገሪቱ የትምህርት ስርዓት ሰላሳ በመቶው ብቻ ነው ለማኅበራዊ ዘርፍ የተሰጠው። ምንም እንኳን በቴክኖሎጂው ዘርፍ አገርን ለማዘመን ታስቦ የተደረገ እንደሆነ ብናስብም፤ ሰዎች በማኅበራዊ አኗኗራቸው ቅርጽና ስርዓት ካልያዙ በቀር ሳይንስ ብቻውን የሚኖረው ፋይዳ ዝቅተኛ ነው። የአገር ፍቅር ከሌላው መሃንዲስ ይልቅ አገሩን የሚወድ አንድ ደራሲ ብዙ መሥራት ይችላል ብል ማጋነን ይሆን ይሆን? ታዲያ ይኸው መድረክ ብዙም ትኩረት ባልተሰጠው በማኅበራዊ ዘርፍ የተሠሩና ከመደርደሪያ ያልወረዱ ጥናታዊ ጽሑፎችንም ያስተናግዳል።

ታሪክን ማወቅ፤ የቀደመው መረዳት ወደፊት ያለውን መስመር ለማስመርና አቅጣጫን መለየት እንደሚረዳ እንተማመናለን። እነዚህ መድረኮች ደግሞ በተለይ በማኅበራዊ ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው ስለመሆናቸው ጥርጥር የለውም። ከዛ ባሻገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ያሉ ይመለከተናል የሚሉ ተቋማት በሳይንሳዊ ጽሑፎች ሳይቀር እጅግ ማራኪና አሳታፊ መድረኮችን ሲያዘጋጁ ለማየት ችለናል።

ይህ ሁሉ እንግዲህ ከባህር በቅርፊት እንዲሉ እጅግ በጣም በጥቂቱ ነው። የተሻለ የሚያውቁ ምሁራን እና የዚህ መድረክ ተሳታፊዎች ከዚህ ላቅ ያለ እና ጠቃሚ አስተያየት መስጠት እንደሚችሉ እርግጥ ነው። ሁላችንንም የሚያስማማን አንድ ጉዳይ አለ፣ ከላይ እንዳልነው የንባብ ባህልን ለማዳበር፣ ለመጠየቅ፣ ለማወቅ፣ በውይይትም ሃሳብን ለማዳበር በፍጹም የማይሸረሸር አስተዋጽኦ አላቸው። ነገር ግን አንድ ነገር ቅር ይላል፣ በእነዚህ መድረኮች ተሳታፊ የሚሆኑት ተመሳሳይና ውስን ሰዎች መሆናቸው ነው።

ብዙ ነገር ከሚገኝበት፣ በለጋስነትም ሃሳብ ከሚሰጥበት፣ በስማቸው ሳይሆን በግብራቸው፣ በሙያቸው የተከበሩ ምሁራን በሚገኙበት መድረክ ላይ ጥቂት ሰው ብቻ ማየት የሚያነሳሳ አይደለም። ቢሆንም ግን ሁሉም ነገር አንድ ብሎ እንደሚጀምር፣ የወሰደውን ጊዜ ቢወስድ ያሉት መድረኮች በርትተው ከቀጠሉ በብዛት የተሻለ ታዳሚ በእነዚህ መድረኮች እንደምናይ እርግጥ ነው። እንዲህም ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በዚህ መጻሕፍትን ጓደኛ ያደረገ፤ የኋላውን ተረድቶ የፊቱን መንገድ የሚያስተካክል ትውልድ ማፍራት ይቻላል። ሰላም!

 

ሊድያ ተስፋዬ

Published in ማህበራዊ
Sunday, 08 October 2017 21:00

ጀፎ'ረ እና ባህላዊ ፋይዳው

የጉራጌ ባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት የሚከወንበት ሥፍራ ወይም ጀፎ'ረ፤

 

የጉራጌ ብሔር እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ለህልውናው ሲል በሚያከናውናቸው ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችና ማህበራዊ ግንኙነቶች እንዲሁም ከአካባቢውና ከተፈጥሮ ጋር በሚያደርጋቸው መስተጋብሮች የፈጠራቸው አሁንም እየተጠቀመባቸው የሚገኙና የማንነቱ መገለጫ የሆኑ አያሌ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ያሉት ነው። ከእነዚህ ቅርሶች መካከል ደግሞ የጀፎ'ረ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት አንዱ ነው።

የጀፎ'ረ ሥርዓት ከጉራጌ ብሔረሰብ ሁለንተናዊ ህይወትና እድገት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ሥርዓቱ ከቀላል የእድገት እርከን ተነስቶ ቀስ በቀስ ትልልቅ ወይም ውስብስብ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓትን እየያዘና ችግሮች ሲፈጠሩም በቀላሉ እየፈታ የቀጠለ ነው። ጀፎ'ረ የጉራጌ ባህላዊ ገጽታዎችን ከማካተቱ ባለፈ ታሪክና እምነትን እንዲሁም አገር በቀል እውቀቶችን አካቶ የያዘ ጥንታዊ የዲሞክራሲ አስተዳደር ሥርዓትም እንደሆነ የአካባቢው ተወላጆች ይናገራሉ።

ጀፎ'ረ ትውልዱን እየተካ የሚጓዝ ሲሆን፤ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና በማህበራዊ መስክ፣ በህግ ህብረተሰቡን የመምራት ኃላፊነት በመስጠት የሚተገበር ነው። ለመሆኑ ጀፎ'ረ ማለት ምን ማለት ይሆን ወደሚለው ስንገባ፤ አንዳንዶች ጀፎ'ረ ማለት መንገድ ወይም ጎዳና ነው ይላሉ። አንዳንድ የባህሉ አባቶች ደግሞ መንገድ የሚለው ትርጉም አይስማማውም ጀፎ'ረ ከዚያ በላይ ትርጉም ይሰጠዋል ይላሉ። ይሁን እንጂ ሁለቱንም የሚያስማማቸው ጉዳይ አንድ ሀሳብ አለ። ይኸውም አገናኝ፣ አስታራቂ፣ መፍትሄ ሰጪ ወይም ደግሞ አስተዳዳሪ የሚለው ነው። እስኪ እያንዳንዱን በተናጠል እንመልከተው።

በመጀመሪያ ጀፎ'ረ ማለት ስብስብ፣ ወይም ህብረት ማለት ነው የሚል አንድምታን የሚሰጡትን አባቶች አመለካከት እንመልከት። በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ማለትም ጎረቤታማቾች በማህበራዊ ግንኙነታቸው የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን ሲፈልጉ በህብረት የሚወያዩበት ስፍራ እንደሆነ ይገልጻሉ። ለአብነት ትልቅ ዋርካ ስር ሊሆን ይችላል። የተሰበሰቡበት ምክንያትም ለምሳሌ በባልና ሚስት መካከል የሆነ ችግር ተፈጥሮ ችግሩን እንዴት ይፈታ ለማለት፤ የድንበር ጉዳይ ችግሮች ሲገጥሙና ሌሎች ችግሮች ሲፈጠሩ የሚደረግ ስብሰባ ነው።

በሌላ መልኩ ደግሞ በዓላትን ለማክበርና እንዴት በዓሉ ይከበር የሚለውን ጉዳይ ለመወያየት በዚህ አይነቱ ስብስብ መድረክን ይፈጥራሉ። በዚህ ወቅት ምንም እንኳን በሌሎች የዳኝነት ሥርዓቶች ላይ ሴቶችና ህጻናት መሳተፍ ባይችሉም፤ የእዚህ ቀን ግን ልዩነት የለም። እንደውም በስፋት ቦታው ላይ ሽር ጉድ ሲሉና የተለያዩ የምግብ አይነቶችን ሲያዘጋጁ የሚታዩት ሴቶች ናቸው። የወደፊት የታሪኩ ተረካቢዎች ህጻናትም ቢሆኑ በዚህ መርሃ ግብር ላይ እንዲኖሩ ይፈቀድላቸዋል። ስለዚህም በዚህ ወቅት ልጆች ባህሉን ለመውረስ፣ አባቶች ምርቃት ለመስጠትና ለአገር ሰላም ለመለመን፣ ሴቶች ደግሞ የፈለጋቸውን ለመጠየቅና ልመናቸውን ለማድረስ ይሰበሰባሉ። በዚህ ቦታ ማንኛውም ሰው ይገኝበታል፤ ድሃና ሀብታም አይለይበትም፤ ያለው ለሌለው ያካፍላል። አለኝ ብሎ የሚንቀባረርና ከሌሎች ጋር ተካፍዬ አልበላም የሚል አካልም አይኖርም። ስለዚህም ይህ ጀፎ'ረ የተባለ ስያሜ የተሰጠው የውይይት ቦታ ሁሉንም በእቅፉ ውስጥ አሰባስቦ ስለሚመከርበት፤ መፍትሄ ስለሚሰጥበት፤ ስዕለት ተስለው ስለሚሄዱበት፤ እንደልመናቸው አይነትም መፍትሄ ስለሚቸሩበት ነው። ያው የእምነቱ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ለዓመቱ ደስታውን ሲገልጽና ስዕለቱን ሲያስገባ የሚታይበትም ቦታ ነው።

ጀፎ'ረን ብዙ ጊዜ ከዳኝነት ሥርዓት ጋር ይገናኛል ይላሉ የእዚህ አመለካከት ባለቤቶች፤ እናም በዚህ ሥርዓት ላይ ሴቶች በባህሉ መሰረት መፍረድ አይችሉም ተብሎ ስለሚታመን እንደነዚህ ዓይነት ሥርዓቶች ላይ እንዲሳተፉ አይፈቀድላቸ ውም። ይሁን እንጂ ተበዳይ ከሆኑና እንደ ምስክርነት ከተፈለጉ ተጠርተው እንዲቀርቡ ይደረጋል። ለእነርሱም ፍትህ ታሰጣለች፤ ችግር ትፈታለች ተብላ የምትታወቅ «አጄት» የምትባለው ሴት ስለምትኖር እርሷ በዚህ ላይ አስተያየቷን እንድትቸር ይደረጋል።

በጉራጌ ባህል «አጄት» ተብላ የምትጠራዋ ሴት እናት አባት የሌላቸውን ወይም ደግሞ የሞቱባቸውን ሰዎች ደግሳ በመዳር የምትታወቅ የጉራጌ ምድር ያፈራቻት ውብና ጠንካራ የእቤት እመቤት ነች። በዘመኑ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የባህል ተፅዕኖና የወንዶች የበላይነት በመቃወም ከአስር በላይ የመብት ጥያቄዎችን ይዛ እንደተሟገተችው የለውጥ አርበኛ ቃቄ ውርዶት አይነት ሴት ስለሆነች በማንኛውም ስፍራ ሴቶችን ወክላ የምትሟገት ትሆናለች።

ይህቺ ሴት እምነት፣ ጎሳና ሌሎች መስፈርቶች አይወጡላትም፤ ብቸኛ መለየዋ ትሁትና ጠንካራ እንዲሁም ሰዎችን ለማገዝ ፈቃደኛ የሆነች መሆን ብቻ መስፈርቷ ይሆናል። በሰዎችም ዘንድ ብዙ ተቀባይነት ሊኖራት ይገባል። ሌሎች አቻዎቿን ጭምር ለለውጥ የምታነቃቃ መሆን ይጠበቅባታል። እናም በትግሏ ሴቶችም ሆኑ ሌሎች አካላት የሚኮሩባት መሆን መቻል አለባት። ምክንያቱም በጀፎ'ረ ላይ ተገኝታ ብዙዎቹን ሽማግሌዎች ማሳመን ስለሚጠ በቅባት፤ በእርግጥ ያለ አግባብ ተግባራት እንዲከወኑ ማድረግ የለባትም፤ ሴትዮዋ ጥፋተኛ ከሆነችም ጥፋቷን ሳትሸፍን ቅጣቱ እንዲቀል ማድረግ ብቻ ነው የሚኖርባት።

ወደ ሁለተኛው አመለካከት ስንገባ ደግሞ የጀፎ'ረ ትርጉም ባህላዊ አውራ መንገድ የሚለውን ይይዛል የሚሉትን እናገኛለን። እነዚህ አባቶች ይህንን ያሉት ለምን ይሆን? ሲባል ምክንያታቸው እንዲህ ነው። ለጉራጌ መንደሮች ትልቅ ውበት መላበስ ምክንያቱም ይኸው ባህላዊ ጀፎ'ረ እና የቤት አሰራሩ ነው። ይህ ደግሞ ምንም አይነት ዘመናዊ የምህንድስና ትምህርት ሳይከታተሉ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎ ቻቸው ይመቻቸው ዘንድ የቀየሱት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው የመንገድ አይነት ነው። ጀፎ'ረ።

አንድ ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች የሚለይበት የራሱ መገለጫ የሆኑ የተለያዩ እሴቶች ይኖሩታል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ህብረተሰቡ ከሚከተለው የህይወት ፍልስፍና እና የአኗኗር ዘይቤው መነሻነት ነው፡፡ እናም የህብረተሰቡ ባህላዊ ስነ-ጥበባት፣ ቁሳዊና ሀይማኖታዊ ክዋኔዎቹ በዋነኛነት በዚህ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። የጉራጌ የመንደር አመሰራረት መሰረት የሚያደርገውም ከዚሁ የተነሳ ነውና ጀፎ'ረን መስርተዋል ይላሉ። ይህም አረንጓዴ ሳር ለብሶ ውብና ማራኪ ገፅታ ያለው እንዲሁም ግርማ ሞገስን ተላብሰው በተገነቡት ባህላዊ ጎጆ ቤቶች ታጅቦ በሁለት መንደሮች መካከል በትይዩ የሚገኝ ከ60 ሜትር በላይ ስፋት ያለው ቦታ መሆኑንም የአካባቢው ነዋሪዎች ያስረዳሉ።

የጉራጌ አውራጎዳና (ጀፎ') አመሰራረት መቼ እንደተጀመረ በውል የተረጋገጠ መረጃ ባይገኝም፤ ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት እንደተጀመረ አንዳንድ የብሔረሰቡ ተወላጅ የሆኑ የእድሜ ባለፀጋ አባቶች ይናገራሉ፡፡ ጀፎ'ረ ለብሔረሰቡ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ በርካታ ዘመናትን የተሻገረ ሲሆን፤ ስለአጠቃቀሙም ቢሆን የብሔረሰቡ ተወላጅ አባቶች ተሰባስበው በመምከር በባህላዊ መልክ የሚዳኝበትን ህግ አርቅቀው ተግባራዊ በማድረጋቸው ዛሬ ድረስ ተጠብቆ ሰፊ ግልጋሎት እየሰጠ እንዲቆይ ሆኗል።

ጀፎ'ረ ባለቤትነቱ የህዝብ አገልግሎቱ ለህዝብ የደህንነቱም ጠባቂ የአካባቢው ህዝብ ነው፡፡ በጉራጌ ታሪክ ጥንት መሬት የሚሸነሸነው በባህሉ በተመረጡ አባቶች (የዥር ዳኘ) የመሬት ልኬት ዳኞች አማካይነት ስለነበር (ጀፎ') ባህላዊ የአውራ መንገድ ልኬት ቅድሚያ ይሰጠው ነበረ፡፡ ጀፎ'ረ በሁለት ትይዩ መንደሮች መሀል የሚያልፍ ወንዝ ገደል ወይም ጥብቅ ደን እስከሌለ ድረስ ሳይቋረጥ የሚቀጥል የመንገድ አይነት ነው ብለው የሚናገሩም አሉ። የጎን ስፋቱም ከ100 እስከ 150 ሜትር ሊደርስ ይችላል ይባላል።

መስቀለኛ መንገዶች በሚያልፉበት አካባቢ እስከ 200 ሜትር ተለክቶ ለወል ግልጋሎት ክፍት ይሆናል። ከዚያ ለባህላዊ አውራ መንገድ የተቀየሰው መንገድ አጥሮ ወደ ግል ግቢ መከለል በምንም መንገድ የተወገዘ ተግባር በመሆኑ በብሔረሰቡ ተወላጆች ዘንድ ለህዝብ አገልግሎት የሚውል አውራ መንገድ በመሆን የተለያዩ ተግባራት ይከወንበታል። ጉራጌ /ለጀፎ'/ ለአውራ መንገድ ትልቅ ትኩረት የሚሰጥበት ዋና ምክንያት በብሔረሰቡ የሠርግ የደስታ የኀዘን እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የጋራ መፍትሄ የሚሰጥበት መንገድም መድረክም ስለሆነ ነው፡፡ ለጋራ ወይም ለወል መሬት እንዲሁ ትልቅ ትኩረት ይሰጣል፡፡

የጉራጌ ጀፎ'ረ በማንም ሳይደፈር ዘመናትን ለማስቆጠሩ ሌላኛውና ትልቁ ምክንያት «ጉርዳ» የተሰኘው ባህላዊ ቃልኪዳን ነው፡፡ በዚህ ቃል ኪዳን ተከብሮ ዘመን የተሻገረው ጀፎረ ለብሔረሰቡ እየሰጣቸው ካሉ አገልግሎቶች መካከል፤ በሠርግ ሥነ-ሥርዓት የሙሽራውና የሙሽሪት አጀቦችና ወገኖች በዘፈን በግጥም የሚሞጋገሱት፣ ሙሽሮች አጋጌጣቸውና ውበታቸው ጎልቶ የሚወጣበት እንዲሁም በሽማግሌዎች ወይም በእናቶችና በአባቶች የሚመረቁበት የተከበረ ተወዳጅ ስፍራ ነው፡፡

ሰው ሲሞት እግረኛና ፈረሰኛ ሙሾ የሚደረድረውና የለቅሶ ሥነ-ሥርዓት የሚያከናውነውም በዚሁ በጀፎ 'ረ ነው፡፡ ሽማግሌዎች ስለ ማህበራዊ ህይወታቸውና አጠቃላይ ኑሯቸው በጋራ የሚመክ ሩበት፣ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት የሚከናወንበት፣ መንገደኛ ያለአንዳች ችግር የሚጓዝበት፤ ህፃናቶች የሚቦርቁበት ጎረምሶችና ኮረዶች በብሔረሰቡ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ዓመታዊ የመስቀልና የአረፋ በዓላትን ተከትለው የሚመጡ የጉራጊኛ ጭፈራዎች የሚከናወኑበት፣ ወጣቶች ፈረስ ጉግስ የሚለማመዱበት፣ በቅሎና ፈረስ የሚገሩበት፣ ከብቶች የሚጠበቁበትና የመሳሰሉት ተግባራት ከብዙ በጥቂቱ ጀፎ'ረ ላይ ይከናወናሉ።

ከጥንት ጀምሮ ጉራጌ በጀፎ'ረ ደስታውንና ኀዘኑን ሲገልጽበት እዚህ ደርሷል፡፡ ቂም በቀሉን ይቅርታ ይጠያየቅበታል፤ ስለሰላሙ ይመክርበታል፤ ስለህይወቱ ይዘክርበታል፤ የተበዳዮችን እንባ ያብስበታል፡፡ ፍትህ ለተነፈጉ ፍትህ ይሰጥበታል፡፡ እምነቱን ይገልፅበታል፡፡ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ይከውንበታል፡፡ በአጠቃላይ ጀፎ'ረ ለጉራጌ ህዝብ ህይወቱ እንደሆነ ማስቀመጥ ይበቃል። እናም እንደ ጀፎ'ረ ያሉ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ህልውና የሚወሰነው ከትውልድ ወደ ትውልድ ይዘታቸውን ጠብቀው መተላለፍ መቻላቸው ላይ ነው። ስለዚህም ሥርዓቱ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን እውቀትና ክህሎት የትውልድ አባላቱ በቅርሱ ትግበራ ላይ ተሳትፎ በማድረግ መቅሰም ይጠበቅባቸዋል። በተለይ ወጣቶች ስለ ሥርዓቱ ታሪካዊ አመጣጥና ለማህበረሰቡ ስለሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ካዩት፣ ከሰሙት በመነሳት ባህሉን ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው። የአካባቢው ሽማግሌዎች የሚሰጡትን የቃል ትምህርት መከተልና ተግባራዊ ማድረግ ላይም መስራት ይኖርባቸዋል።

ጀፎ 'ረ በባህሉ ዘንድ እጅግ ከሚወደዱ ሥርዓቶች አንዱ ሲሆን፤ ፋይዳውም እጅግ ሰፊ ነው። እናም የጀፎ'ረ መኖር ፍትህ የሚጀመርበት በመሆኑ ከሥሩ ችግሩን ለማድረቅ ያገለግላል፤ ይህ ደግሞ ፍርድ ቤት ሥራውን እንዲቀንስ፣ ሌሎች ችግራቸው የገነነባቸው ሰዎች በአፋጣኝ መፍትሄ እንዲያገኙ፤ ዳኞችም ፋታ እንዲያገኙ ያግዛል። በሌላ በኩል ደግሞ በጀፎ'ረ የሚሰበሰበው ሽማግሌ ሃይማኖትን የለየ ስላልሆነ ሁሉም ባለው ሃይማኖት ስለሚያምን ችግሩ በባህሉ መሰረት እንዲሆንና ለፍርዱ ትኩረት እንዲቸረው እንዲሁም ራሱን ለህግ ተገዢ እንዲያደርግ ይረዳል።

ሰውም ቢሆን የአገር ሽማግሌዎች ምን ያህል ዋጋ እንዳላቸው እንዲማር ያግዛል። ልጆችም እንዲሁ ስለ ፍትህ ምንነት እንዲረዱ መንገድ የሚከፍት ነው። ጀፎ'ረ የቤተሰብ ትስስር እንዲጠናከርም ያደርጋል፤ በአገር ላይ ያለውን የፍትህ ጫናም ይቀንሳል። እናም መንግሥትም ቢሆን እነዚህ አይነት ባህሎችን በመደገፍ ለአገሪቱ ሰላም ማስጠበቅ ከፍተኛ ፋይዳ መኖራቸውን ተገንዝቦ መንከባከብና ትኩረት መቸር አለበት በማለት ለዛሬ የያዝኩትን ሀሳብ ልቋጭ። ሰላም!

 

ጽጌረዳ ጫንያለው

Published in ማህበራዊ

 

ኢትዮጵያ ድርቅን ለመከላከልና ድርቅ በሚያጋጥማት ወቅትም ከተረጂነት ለመላቀቅና ራሷን ችላ ከችግሩ ለመውጣት አቅሟን እያዳበረች ትገኛለች፡፡ ይህ የሆነውም የግብርና ምርትንና ምርታማነቷን ማሳደግ በመቻሏ ነው፡፡ ይህ የተፈጠረ አቅም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መላው የአገራችን ህዝብ ግብርናን በማዘመን፣ የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ እንዲሁም በመንከባከብና ለአፈር እና ለውሃ ጥበቃ የተሰጠውን ትኩረት ማጎልበት ይኖርበታል፡፡

እስካሁን ድረስ የተደረጉት ጥረቶች አገራችን ውስጥ የተፈጠሩ የድርቅ አደጋዎችን መቋቋም የቻሉ ናቸው። እንደሚታወቀው ከታዳሽ ኃይል በተለይም ከውሃ ኃይልን በማመንጨት በተነጻጻሪ ከሌሎች ሀገራት ቀድማ አረንጓዴ ልማትን መተግበር የጀመረችው ኢትዮጵያ፣ ሀገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ያላትን ተጋላጭነት ለመቋቋም የአረንጓዴ ልማት ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ መቅረጿ አይዘነጋም፡፡

ከአረንጓዴው ልማት ስትራቴጂ መሰረቶች ውስጥ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን፣ የደን ልማት፣ ታዳሽ ኃይል አማራጭ መከተል እንዲሁም የትራንስፖርት፣ የኢንዱስትሪ የቤት ልማትን በተስማሚ ቴክኖሎጂ መተግበር የሚሉት ጉዳዮች በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው። የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ፣ ኢትዮጵያ ያቀደችውን የተለጠጠ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳካትና የሙቀት አማቂ ጋዞችን መቀነስ የሚያስችሉ አማራጮችና ዕድሎችን መለየት ዋናው ዓላማው ነበር፡፡ መንግሥት በዘርፉ የተሻለ ልምድ ያላቸውን የልማት አጋር አካላትን ለመሳብ ጥረት እንደሚደረግም ስትራቴጂው ያመለክታል፡፡

የልማቱ አማራጭ አብዛኛውን የአገሪቱን ጠቅላላ ምርት ነዳጅና ተመሳሳይ የኃይል ምንጮችን ከውጭ በማስገባት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ሀገሪቱን ለውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ይዳርጋታል፡፡ ከታዳሽ ኃይል በተለይም ከውሃ ኃይልን በማመንጨት በተነጻጻሪ ከሌሎች ሀገራት ቀድማ አረንጓዴ ልማትን መተግበር የጀመረችው ኢትዮጵያ፣ ሀገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ያላትን ተጋላጭነት በፍጥነት የአረንጓዴ ልማት ማስፈጸሚያ ስትራቴጂ ቀርጻለች፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን፣ የደን ልማት፣ ታዳሽ ኃይል አማራጭ መከተል እንዲሁም የትራንስፖርት፣ የኢንዱስትሪ የቤት ልማትን በተስማሚ ቴክኖሎጂ መተግበር የአገሪቱ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂው መሰረቶች ናቸው፡፡ የስትራ ቴጂው መሰረቶች አተገባበር እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

የመጀመሪያው የስትራቴጂው መሰረት የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን ነው፡፡ ዘርፉ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሪ ዘርፍ መሆኑና የአብዛኛው የሀገሪቱ ዜጎች መተዳደሪያ መሆኑ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ ከዚህ ቀደም በተለምዶ እንደሚደረገው የሚታረስ መሬትን ማስፋፋትና የቀንድ ከብቶችን ቁጥር ከማሳደግ ይልቅ የመሬትንና የቀንድ ከብቶችን ምርታማነት ማሳደግ የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫ ነው፡፡

የተሻሻሉ የሰብልና የቀንድ ከብት ዝርያዎችን አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ማድረግ የግብርና ዘርፍ ማሳደጊያ ስልት ነው፡፡ የደን ጭፍጨፋን ለመቀነስ በተለይም በተራቆቱና በተጎዱ አከባቢዎች ዝቅተኛ፣ መካከለኛ እንዲሁም ከፍተኛ የመስኖ ልማት ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት ጥረት ተደርጓል፡፡ እነዚህ ጥረቶች ድርቅን የመቋቋም አካል ናቸው፡፡

እርግጥ በተፈጥሮ የአየር መዛባት ምክንያት በሀገራችን የድርቅ አደጋ ሲከሰት አዲስ ነገር አይደለም። ይህ ደግሞ በተፈጥሮ ችግር ምክንያት የሚከሰት ጉዳይ በመሆኑ ምንም ማድረግ አይቻልም። ሆኖም ይህ በየጊዜው ሀገራችንን የሚጎበኛት የድርቅ አደጋ ወደ ረሃብነት እንዳይቀየር መንግስት ብርቱ ጥረት አድርጓል።

እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት የመንግሥት ትኩረት ምንም ዓይነት የአየር ንብረት መዛባትና ድርቅ ቢያጋጥምም፤ ህዝባችን የማይራብበት ሁኔታን በመፍጠር ላይ ሲረባረብ መቆየቱ አይዘነጋም። የኤልኒኖ አደጋ በተከሰተበት ወቅትም አደጋውን በመቀልበስ የልማት አጋር ሀገራትን ድጋፍ እምብዛም ሳያገኝ ችግሩ ወደ ረሃብነት ሳይቀየር መቋቋሙ ይህን ጥረቱን አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን ከማንም የተሰወረ ጉዳይ አይመስለኝም።

በእኔ እምነት መንግሥት ከአጭር ጊዜ አኳያ በተፈጥሮ ችግር ምክንያት የሚከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል በፍጥነት በመድረስና ዕርዳታ ማድረግ እንዲሁም ድጋፉ ልማታዊ በሆነ አኳኋን ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጉ ለዜጎቹ ያለውን የኃላፊነትና የተጠያቂነት መንፈስ ስሜትንና ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ነው።

አርሶ አደሩ ከራሱ ተርፎ ለገበያ በማምረት ተጠቃሚ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ ሀገሪቱም ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ጎዳና እንዲፈጠር አድርጓል። ለዚህ ስኬት በመንግሥት በኩል የተወሰዱት እርምጃዎች በቂ ማሳያዎች ናቸው ማለት ይቻላል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ ለእርሻ የሚውል ሰፊ መሬት አላት። ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች በአርሶ አደሩ እጅ እንዳለ የሚታሰበው መሬት አነስተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ካለችውም መሬት ቢሆን የሚያገኘው ምርት ዝቅተኛ ነው። አመራረቱም እጅግ ኋላ ቀር ሆኖ ቆይቷል።

ይህን ዕውነታ የተገነዘበው የኢፌዴሪ መንግሥት ዘርፈ ብዙ የማሻሻልያ ጥረቶች አድርጓል። በውጤቱም አነስተኛ ይዞታ ባላቸው አነስተኛ የአርሶ አደሮችን ማሳ ላይ ለውጥ ማምጣት አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ ሰብሯል። አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ለሰፋፊ እርሻዎች ትኩረት መስጠትና ለውጥ ማምጣትን የሚሰብኩ ወገኖችን አፍ ማስያዝ የቻለ ትክክለኛ መስመርን በመከተል ውጤት ማምጣት ችሏል።

በአርብቶ አደሩም አካባቢ ተመሳሳይ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በመቅረፅና ወደ ተግባር እንዲገባ በማድረግ ድርቅ ሊፈጥር የሚችለውን አደጋ በአያሌው መቀነስ ተችሏል። ከእነዚህ መንግሥታዊ ጥረቶች ውስጥ የአርብቶ አደር የልማት ፓኬጆችን በመቅረፅ ውጤታማ ስራ ተከናውኗል።

አርብቶ አደሩ ከልማዳዊ የአኗኗር ባህል ወጥቶ ወደ ዘመናዊ ህይወት እንዲቀየር፣ ከአርብቶ አደሩ ጋር በመነጋገር ድርቅን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችሉ የመስኖ ልማት ስራዎችን በማስፋፋት ወደ ከፊል አርሶ አደርነት እንዲሸጋገር ብሎም ምርጥ ዝርያዎችን አግኝቶ ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ፣ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃዎችን በአግባቡ የማሰባሰብ ስራዎችን እንዲያጠናክርና ሌሎች መሰል ተግባራቶች ተከናውነዋል።

ሆኖም አሁንም ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም ሌሎች ተግባሮች መፈፀም አለባቸው። በአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂው መሰረት ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ማስፋት ያስፈልጋል። ምርትና ምርታማነት ሲሰፉና ሲጎለብቱ የድርቅ አደጋ በሚያጋጥምበት ወቅትም ቢሆን ትርፍ ምርት ለመያዝ ይቻላል። በመሆኑ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተግባሩን መከወን የድርቅ አደጋን ለመከላከል የሚያስችል ይሆናል፡፡

 

ታዬ ከበደ

Published in ፖለቲካ

አቶ መሀመድ ኮርንማርን ፤

 

ዓለምን የለወጣት፣ አሁን የደረሰችበትንም ደረጃ ያቀናጃት ግልጽ ውይይቶች እየተደረጉ የአስተሳሰብ ለውጦች በየጊዜው እየመጡ በመሄዳቸው የተነሳ እንደሆነም ብዙዎችን የሚያስማማ ሀቅ ነው። ስለዚህም ይህ እድገት በአገር ደረጃ እንዲመጣ ከተፈለገ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ማምጣት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑ እሙን ነው። በእርግጥ ማህበረሰቡ ከማን ይማር ከተባለ ደግሞ ትምህርት መስጠቱ ከተማረውና ከአመራሩ ይጀምራል። ለእዚህም ይመስላል ዛሬም በጥንቱ እሳቤና ቀመር የሚያሰሉ ሰዎች እንዳይኖሩና እንዲለወጡ ለማድረግ ጭምር መንግሥት በየደረጃው ጥልቅ ተሀድሶ ማካሄዱ።

ኅብረተሰቡ የደረሰበትን የእድገት ደረጃ፣ የአስተሳሰብ ምጥቀትና የእውቀት ክህሎት የቴክኖሎጂውን ልቀት የተረዱ ከአካባቢያችንና ከዓለም ፈጣን ለውጥ አንጻር አመለካከትና ቅኝታቸውን እንዲያስተካክሉ እንዲሁም ለመብቱ የሚታገል ንብረተሰብ እንዲፈጠር እንዲህ አይነት ተግባራት ያስፈልጋሉ። እናም ይህንን ለማድረግ በአገር አቀፍ ደረጃ የጥልቅ ተሀድሶ ተግባራት ሲከወኑ ቆይተዋል። ታዲያ ይህ ተግባር ምን ውጤት አስገኘ? እውን ታድሰውበታል? ዛሬ ላይስ ምን እየተከናወነ ነው ስንል የጉራጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ኮርንማርን አነጋግረን አጠር ያለ ቆይታ አድርገናል። ቃለ ምልልሳችንንም እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤ መልካም ንባብ።

 

አዲስ ዘመን፡- በዞኑ በዋናነት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ናቸው የሚባሉት የትኞቹ ናቸው?

አቶ መሀመድ፡- 2009 .ም ሁሉም እንደሚያውቀው በአገር ደረጃ የተሀድሶ መድረክ ተፈጥሮ ነበር። በዚህም እንደ አገር የተለዩ ችግሮችን በክልልም ሆነ በዞን ደረጃ ለማየት ተሞክሯል። ይህ ደግሞ ሰፊ ክፍተትን የዳሰሰና ያስተማረን ነበር። እናም ከክልሉ ውጪ ዞኑን ብቻ ይመለከታሉ ተብለው የተለዩ ዋና ዋና ጉዳዮች አሉ። እነርሱም ሲቪል ሰርቪሱና አመራሩ ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ማድረስ አለመቻሉ፣ የአመለካከት ችግሮች፣ ብልሹ አሰራሮች መንሰራፋታቸው ይጠቀሳሉ።

በተለይ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተፈታ የመጣ ቢሆንም በቅጥር፣ በዝውውርና በደረጃ እድገት ላይ የሚታዩ አድሏዊ ተግባራት ዞኑን ከፈተኑት ጉዳዮች መካከል የሚነሳ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የገጠርና የወል መሬቶችን ያለ አግባብ መውሰድ በከተማም ለቤት ልማት፣ ለኢንዱስትሪና ለአገልግሎት ዘርፍ መቅረብ የሚገባውን መሬት ለማይገባው አካል ይሰጥ ነበር። ግዥ ውስጥ የሚፈጸሙ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ለሥራ መጓተትና የጥራት ችግሮችን የፈጠረም ስለነበር መንግስት ባወጣው መመሪያ መሰረት ካልተከናወነና በግልጽ ጨረታ ካልተሰራ የመልካም አስተዳደር ችግር ይሆናልና ይህም በወቅቱ ከተለዩት ችግሮች መካከል አንዱ ሆኗል። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ የተጣሉ ግቦችን ያለማሳካትና ዝቅተኛ አፈጻጸም መኖር ሌላው ችግር ነበር።

አዲስ ዘመን፡- እነዚህን ችግሮች ከለያችሁ በኋላ ምን መፍትሄ ወሰዳችሁ?

አቶ መሀመድ፡- በየደረጃው የተለያዩ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ተደርጓል። ለአብነት ከኮንትራት አስተዳደር ጋር ተያይዞ ለሚፈጸሙ ብልሹ አሰራሮችና መሬት ላይ የሚሰሩ መስሪያ ቤቶችን በስፋት በማየት የችግሩ ሰለባ በመሆናቸው ተረጋግጧል። በዚህም ደግሞ የተሰጣቸውን ግብ ማሳካት ካልቻሉ መሥሪያ ቤቶች መካከልም የሚጠቀሱ ናቸው። በመሆኑም በየደረጃው ያሉት ሠራተኞች ላይ እንደጥፋቱ ክብደትና ቅለት እርምጃ ተወስዷል። ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከልም ከሥራ መሰናበት፣ አመራሮችን በሌላ አመራር የመተካት፣ ካሉበት እርከን ዝቅ ማድረግና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ከዚህ ባለፈ ደግሞ ያላግባብ የተወሰዱ መሬቶችን ወደ መሬት ባንክ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ፤ ከኮንትራት አስተዳደር ጋር ግንኙነት ያላቸውን አመራሮች እጃቸውን እንዲሰበስቡ ለማድረግ ማንኛውም በዚህ ሥራ ላይ ልሰማራ ብሎ የመጣ አካል በግልጽ ጨረታ እንዲሳተፍ የማድረግ ተግባርም ተከናውኗል።

አዲስ ዘመን፡- በዞኑ ከተካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ በኋላ ምን ለውጥ መጣ? ማሳያዎቹስ ምንድን ናቸው?

አቶ መሀመድ፡- በዋናነት የተዛባ አመለካከትን የመቀየሩ ተግባር ነው ትኩረት ተችሮት ሲሰራበት የቆየው። ይሁንና በአንድ ጀንበር ውጤታማ ይኮንበታል ተብሎ አይታሰብም። እናም በተሃድሶው እርምጃ መወሰዱና ትክክለኛ አሰራርን ሳይከተሉ የቆዩ ሰዎች ባሉበት ሁኔታ ያለመዝለቃቸው ማህበረሰቡ ላይ ያለን አመኔታ እንዲሰፋ አስችሏል። ችግሩንም ያለምንም ማቅማማት እንዲናገርና እንዲታገል መንገድ ከፍቶለታል። ይህ ደግሞ የተሃድሶው ውጤት ነው።

በእርግጥ ዛሬም ያለፈውን ሥራ የማይደግም አመራር አለ ብሎ ማመን ይከብድ ይሆናል። ነገር ግን ይህ መድረክ መፈጠሩ የእርስ በእርስ መተጋገል መንፈስን እንዲዳብር እንዳደረገው ዛሬ ላይ በሚታዩ አንዳንድ ምልክቶች ማወቅ ተችሏል። አመራሩም ቢሆን ካለፈው ሰው ስለሚማር ዳግመኛ ይህንን ችግር ቢፈጥር ምን አይነት ጉዳት እንደሚገጥመው ስለሚረዳ የተፈለገውን ተግባር ይከውናል የሚል እምነት አለኝ። በትንሹም ቢሆን አሁን እየታየ ያለው ይኸው ክንውን ነው።

ሌላው የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች ውጤታማ ናቸው አይደሉም የሚለውን በጥልቀት ማየት ያስቻለ ነበር። በተለይም ውጤታማ ያልነበሩት በምን መልኩ እንደነበር ያመላከተና ውጤታማ ያደረጉ ዘርፎች ምንድንናቸው? ቀጣይነታቸውስ እንዴት ይረጋገጥ የሚለውን ያሳየን ስለሆነ ጥልቅ ተሀድሶው ለውጦችን አምጥቷል ባይ ነኝ። ለምሳሌ ዞኑ ውጤታማ የነበረበት ሥራ የግብርናው ዘርፍ ነው። በዚህም ብዙኃኑ የጉራጌ ብሔረሰብ ተጠቃሚ ሆኗል፤ ይህ የተደረገው ደግሞ ባለሙያዎች በዞኑ ውስጥ ባሉ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በመዘዋወር ከፍተኛ ጥረት በማድረጋቸውና ከገበሬው እኩል መስራት በመቻላቸው ነው። የመስኖ ልማትም እንዲጠቀሙ በማድረጉ ዙሪያ ሰፊ ሥራ በመሠራቱ ማህበረሰቡ በኢኮኖሚው እንዲያድግና ችግሩን እንዲያቃልል አግዟል።

አዲስ ዘመን፡- ብዙ ጊዜ ተሃድሶ ሲባል አመራሩንና መንግስት ሰራተኛውን ብቻ ትኩረት ያደረገ እንደሆነ ይታሰባል። እርሶ ይህንን እንዴት ያዩታል?

አቶ መሀመድ፡- ተሀድሶ ማለት የውስጥ መታደስ፤ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት፤ አዲስ መሆን ወይም መለወጥ የሚለውን አንድምታ ይይዛል። ይህ ሲባል ደግሞ መለወጥ ያለበት አንድ አካል ብቻ እንዳልሆነ የሚያስገነዝብ ነው። እናም ተሀድሶው በህዝብ ሊታገዝ ፣ ሊደገፍና ሊበረታታ ይገባዋል፡፡ አመራሮችን ማንሳትና መለወጡ የሰው ለውጥ ሊሆን ነው የሚችለው፡፡ ትልቁና መለወጥ ያለበት መሰረታዊ ነገር አስተሳሰብ ነው። ዓለምን የለወጣት፣ የደረሰችበትም ደረጃ እንድትደርስ ያደረጋት የሰው አስተሳሰብ ነው፡፡ መሰራት ያለበትም የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲመጣ ለማድረግ ነው፡፡ ማህበረሰቡና የግል ባለሀብቱ እንዲሁም ከተጠቀሱት አካላት ውጪ የሆኑት ሰዎች የማይለወጡ ከሆነ ምንም አይነት ለውጥ አይመጣም።

ምክንያቱም ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ አይወጣም አይደል ነገሩ፤ እናም የአንድ አካል መለወጥ የአገርን ለውጥ ያመጣል ተብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም። ስለዚህም ሁሉም የአገሪቱ ዜጋ በዚህ የተሀድሶ መስመር ውስጥ ማለፍና እራሱን ማደስ ይገበዋል። እናም በዚህ በዞናችን ያደረግነው ከላይኛው አመራር ጀምሮ እስከታችኛው ማህበረሰብ ድረስ በየዘርፉ በተሀድሶ ውስጥ የሚያልፉበትን መስመር ዘርግተን ሁሉም ራሱን እንዲያይ በቀጣይም ያደረግንበት እንደነበር ማንሳት እወዳለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ይህ ከሆነ በሥራ እድል ፈጠራ ወይም በጥቃቅንና አነስተኛ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚሠሩ ወጣቶችን በምን መልኩ እንዲደራጁ ይደረግ ነበር? ውጤታማነታቸውስ እንዴት ይለካል?

አቶ መሀመድ፡- እንደተባለው በጥቃቅንና አነስተኛ የሚደራጁ ወጣቶች በዞኑ ስፋት ያለው ቁጥርን ይይዛሉ። ጥሩ አፈጻጸም አላቸው። ይሁን እንጂ ጥልቅ ተሀድሶው ከመደረጉ በፊት ችግሮች ነበሩበት። አብዛኞቹ የሚደራጁት ወጣቶች በዝምድና የሚገቡ ናቸው። የውሸት ማህበራት ይፈጠሩናም ለሴቶችና ለወጣቶች ተብሎ የተቀመጠውን ሀብት የመቀራመት አዝማሚያ ይታይ ነበር።

አገሪቱን ሊለውጥ የሚችል ዘርፍ ላይ መሰማራት ሲቻል ከአመራሩ ጋር እየተሳሰረ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ መሰማራትን ማሰብ እንዲሁም ያለ ልፋት ሀብት ማግበስበስ የሚቻልበትን ዘዴ በመፈለግ መግባት በዋናነት ይህንን ዘርፍ ተጠናክሮ እንዳይቀጥል አድርጎታል። ጅማሮው ግን ጥሩ አካሂድ ነበረው። እናም አስተዳደሩ ከጥልቅ ተሀድሶው በኋላ ችግሩን ለይቶት ስለነበር የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ዘርፉ ወደነበረበት አቋም እንዲመለስ ተደርጓል።

ለአብነትም የውሸት ማህበራትን በማፍረስ፣ ትክክለኛ ሥራ ሊያገኝ የሚገባውን ኃይል በሚገባ መልምሎ በሥራው ውስጥ እንዲሰማራ በማድረግ፣ በአካባቢው ምን ቢሰራ አዋጭነት አለው የሚለውን በማስጠናት በዚያ ዘርፍ ወጣቶቹ እንዲሰማሩ እድሉ ተመቻችቷል። በዚህም ዛሬ ላይ ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚሆኑ ወጣቶች እየተበራከቱ ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ ያለውን ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች ይበልጥ ከማስረጽ አኳያ ምን እየተሰራ ነው?

አቶ መሀመድ፡- የጥልቅ ተሀድሶ መድረኩ ብሉሹ አሰራሮች የመከኑበት፤ ልማታዊ አስተሳሰቦች እንዲያድጉ የተደረገበት ስለነበር በየዘርፉ ያለው አመራር በትጋት እየሰራ ይገኛል። በተለይም ማህበረሰቡ ሰላማዊ እንዲሆን እና ልማቱን በሚገባ እንዲያፋጥን በማድረጉ ዙሪያ ከፍተኛ ትግል እየተካሄደ ነው። ለአብነትም ከስልጤዎች ጋር በነበረው ያለመግባባት በዞኑ ይታዩ የነበሩ ክፍተቶችን ለመድፈን የተሰሩ ተግባራት አሉ። ሁለቱ አካላት ሰፊ የውይይት መድረክ ፈጥረው መግባባት ላይ እንዲደርሱ ሆኗል።

ዛሬ ላይም በአንድነት በመተሳሰብና በመከባበር የመሥራት አቅማቸውን እየገነቡ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ ከዞኑ አልፎ ለአገርም ደህንነትና ልማት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። እናም ዞኑ አሁን ላይ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች ያሉበት ነው፤ ምንም አይነት ችግር እንዳይፈጠርም ከጸጥታ ኃይሉና ከኮማንድ ፖስቱ ጋር እንዲሁም ከማህበረሰቡ ጋር በጥምረት እየተሰራ ይገኛልም።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ።

አቶ መሀመድ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

 

ጽጌረዳ ጫንያለው

 

 

Published in ፖለቲካ

 

የመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር ስርዓቱ ውስጥ ካሉ ትላልቅ የምርምር ማዕከላት አንዱ እንደመሆኑ በዘርፉ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶክተር አሕመድ ዩሱፍ ይናገራሉ፡፡ ዶክተር አሕመድ፣ የአርሶ አደሮች የመስክ ቀንን ምክንያት በማድረግ ሰሞኑን በምስራቅ ሸዋ ዞን በተለይም አዳሚ ቱሉ ጅዶ ኮምቦልቻ እንዲሁም ዱግዳ ወረዳዎች ላይ የተከናወኑ የሰርቶ ማሳያ የአርሶአደር ማሳዎችና የልማት ጣቢያዎች በተጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የማዕከሉ ኃላፊነት በዋናነት ዝናብ አጠር ለሆኑ የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የተሻለ ቴክኖሎጂዎችን ማውጣት፣ ማስተዋወቅና መነሻ ዘር በማውጣት ለተጠቃሚዎች ማድረስ ነው፡፡

እንደ ዶክተር አሕመድ ገለጻ፤ ማዕከሉ በአገር አቀፍ ደረጃ የቆላ ጥራጥሬ፣ የግብርና ሜካናይዜሽን፣ የአትክልትና ፍራፍሬን የመሳሰሉ ዘጠኝ ብሄራዊ ፕሮግራሞችን ያስተባብራል፡፡ በእነዚህም ከፍተኛ ቴክኖሎጂዎችን እያወጣ ክልል ለሚገኙ የምርምር ኢንስቲትዩቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ለዘር አባዢዎች የመነሻ ዘር ይሰጣል፡፡ ምርምርና ልማት ለብቻ ሊሰሩ ስለማይችሉም፤ ማዕከሉም ለምርምር ስራው ከፍተኛ አስተዋጽዖ ካላቸውና ድጋፍ ከሚያደርጉ በአገር አቀፍ፣ በአህጉር እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉት ባለድርሻዎች ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም በርካታ የምርምር ውጤቶችን ወደ አርሶአደሩ ያደረሰ ሲሆን፤ በዕለቱም የተለያዩ የበቆሎና ቦሎቄ ዝርያዎችን የእርሻ ድግግሞሽን በመቀነስ ማልማትና ውጤታማ መሆን የሚቻልበትን አሰራር ዕውን በማድረግ የተከናወነው ስራ ነው እንዲጎበኝ የተደረገው፡፡ ይሄም አርሶአደሩ በቃል ከሚነገረው ይልቅ በተግባር አይቶ የተሻለ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችለው ነው፡፡

አቶ ፈዬራ መርጋ በማዕከሉ ተመራማሪ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ማዕከሉ በምርምር እያወጣ ለአርሶአደሩ ከሚያደርሳቸው ቴክኖሎጂዎች መካከል በእለቱ የተጎበኘው በአነስተኛ የእርሻ ድግግሞሽ ምርጥ የበቆሎና የቦሎቄ ዝርያዎችን አሰባጥሮ በመዝራት ውጤታማ የመሆን ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ የእርሻ ድግግሞሽን በመቀነስ የመሬትን ከአፈር መከላት ይከላከላል፤ ተረፈ ምርትንም መሬቱ ላይ በመተው የመሬትን ለምነት ይጠብቃል፤ እያፈራረቁና እያቀላቀሉ በመዝራት እንዲሁም ኬሚካሎችን በመጠቀም አረምን ለመከላከል ያስችላል፡፡

እንደ አቶ ፈዬራ ገለጻ፤ በአካባቢው የተለመደው እርሻን እንደ አፈሩ ሁኔታም እስከ ስድስትና ሰባት ጊዜ ደጋግሞ በማረስ መዝራት ነው፡፡ የተለመደው የሰብል አይነትም በቆሎ ወይም ጤፍ ነው፡፡ ሁሌ እንዲህ ሲሆን ደግሞ መሬት ለምነቱን ይቀንሳል፤ የሰብል በሽታም ይከሰታል፡፡ ደጋግሞ ማረስ አረምን ለመከላከል ሲባል ቢሆንም፤ ይህ አስተራረስ በመሬት ላይ ጉዳት ከማስከተሉም በላይ ጉዳቱን ለመረዳትም ሆነ ከጉዳቱ እንዲያገግም ለማድረግ እስከ 50 ዓመት የሚደርስ ረዥም ጊዜ ይወስዳል፡፡

በመሆኑም ይህ ፕሮጀክት ላለፉት ሰባት ዓመታት በመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል አማካኝነት በአራት ወረዳዎች በአርሶአደሮች ማሳ ላይ ተሞክሮ ያለውን ውጤት በመለየት የተተገበረና ለማስተዋወቅ ወደ አርሶ አደሩ ማሳ የመጣ ነው፡፡ በዚህም በተለይ በቆሎና ቦሎቄን በማሰባጠርና በማፈራረቅ መዝራት ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ደጋግሞ ማረስን ማስቀረቱ ምርትን ሳይቀንስ ወጪን ይቀንሳል፤ የአፈር ለምነትን ጠብቋል፤ እርጥበትን ለማቆየትም አግዟል፤ አካባቢው ዝናብ አጠር እንደመሆኑ ምርጥ ዘሮቹ እስከ 110 ቀናት ውስጥ የሚደርሱ በመሆናቸው ለአካባቢው ተስማሚ በሆነ መልኩ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ዝርያዎቹም በፕሮቲን የበለጸጉ በመሆናቸው አርሶአደሩ ለራሱም ሆነ ለልጆቻቸው በመመገብ ወተትን መተካት ያስችለዋል፡፡

በዱግዳ ወደራ የበቀሌ ግሪሳ ቀበሌ የልማት ሰራተኛ የሆነው አቡ ቢዮ በበኩሉ እንደሚናገረው፤ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ እንዲሁም ተጠቃሚነቱን ከማረጋገጥ አኳያ በቀበሌው በሚገኝ ግሪሳ የልማት ጣቢያ በርካታ የስንዴ፣ የጤፍ፣ የበቆሎና ቦሎቄ ዝርያዎች ምርጥ ዘሮች ከመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመቀናጀት እየለሙ ይገኛል፡፡ በጣቢያው የሚከናወነው ተግባር አርሶአደሩ ምርጥ ዘሮቹን መዝራት ብቻ ሳይሆን እንዴት ግብዓት መጠቀም እንዳለባቸው፣ እንዴት በመስመር መዝራት እንደሚገባቸውና ሰብሎችንም እንዴት አሰባጥረው መዝራት እንደሚችሉ በተግባር የሚማሩበት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ አርሶአደር የማዳበሪያና ኮምፖስት አጠቃቀሙ፣ በመስመር ሲዘራ በምን ፍጥነት ዘር እየጣለ መራመድ እንደሚገባው፣ በቆሎን ከቦሎቄ ጋር እንዲሁም በቆሎም ከእንስሳት መኖ ጋር እንዴት አቀላቅሎ መዝራትና ውጤታማ መሆን እንዳለበት በተግባር እያየ የሚማርበትና ወደራሱ ወስዶ ተግባራዊ የሚያደርግበትን እድል የሚፈጥርለት ነው፡፡ ሆኖም ከጊዜ ወደጊዜ እየጎለበተ የመጣውን የአርሶአደሩን ቴክኖሎጂ የመጠቀም ዝንባሌ የበለጠ መደገፍና ማሳደግ ይገባል፡፡

በዚህ ዙሪያ አስተያየታቸውን ከሰጡን የዞኑ አርሶ አደሮች መካከል በአዳሚ ቱሉ ጅዶ ኮምቦልቻ ወረዳ የኦዳ አንሹራ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ዋዶ አኖሎ አንዱ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ማዕከሉ ያቀረበላቸውን የበቆሎና ቦሎቄ ምርጥ ዘር በመጠቀም ለውጥ እያዩ ናቸው፡፡ አሰራሩም ቀላልና በአነስተኛ ጉልበትና ወጪ የተሻለ ውጤትና ጥቅም የሚገኝበት ነው፡፡ የእርሻ ድግግሞሽን በማስቀረት መሬቱን እንዳይሸረሸር እና እርጥበቱን ጠብቆ እንዲቆይም አድርጎላቸዋል፤ በቆሎና ቦሎቄን አሰባጥሮ በመዝራትም የሁለት ቦታ ዝግጅትን ወደ አንድ በማድረግ ምርታማነታቸውን አሳድጎላቸዋል፤ ዝርያዎቹም ፈጥነው የሚደርሱ፣ ድርቅና በሽታን የሚቋቋሙ እንደመሆናቸውም ለአካባቢው ተስማሚ ናቸው፡፡ በይዘታቸውም በፕሮቲን የበለጸጉ፣ ወተትና ስጋን የሚተኩ መሆናቸው ስለተነገራቸውም ለምግብነት መርጠዋቸዋል፡፡ ቴክኖሎጂዎቹን ለመጠቀምም አርሶ አደሩ ፍላጎት አድሮበታል፡፡

አርሶ አደር ዋዶ እንደሚናገሩት፤ ይህ ውጤታማነት እንደተጠበቀ ሆኖ ዘንድሮ የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ ስለሚያምኑ ምርት በመሰብሰብና በማከማቸት ሂደት ችግር ይገጥመናል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ አንድም የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን በእነርሱ አካባቢ ባለመኖሩ ሲሆን፤ ሁለተኛም ምርታቸውን አከማችተው የሚያቆዩበት ዘመናዊ ጎተራ ባለመኖሩ ከቆየ በነቀዝ እንዳይበላባቸው በማሰብ ነው፡፡ ቶሎ እንዳይሸጡትም የምርት ወቅት ላይ ነጋዴ ዋጋ ስለሚያራክስባቸው፤ የሚመለከተው አካል በምርት ስብሰባም ሆነ በክምችት ወቅት ለሚገጥማቸው ችግር መፍትሄ ሊያደርግላቸው ያስፈልጋል፡፡

ይሄን አስመልክቶ የምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርናና ገጠር ልማት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አሕመድ ሰይድ እንደተናገሩት፤ አርሶ አደሮቹ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢ በመሆናቸው በአግባቡ ተመልክተው የሚሰሩባቸው ይሆናል፡፡ ምክንያቱም አርሶ አደሩ ምርታማ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን ምርቱን በሚሰበስብበትና በሚያከማችበት ሂደት ላይም ሊደገፍ ይገባዋል፡፡ ለዚህም ጽህፈት ቤቱ ከባለድርሻዎች ጋር እየሰራ ሲሆን፤ እንደ ዘንድሮ አይነት ምርት በሚገኝበት ወቅት በምርት ስብሰባና በድህረ ምርት ክምችት ረገድ የሚስተዋል የመፈልፈያና የማከማቻ ችግር ለመፍታትም ቴክኖሎጂውን ከሚያቀርቡ አካላት ጋር የማገናኘትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ በመሆኑም ዘንድሮ የሚጠበቀውን ከፍተኛ ምርት ሳይባክን አርሶ አደሩ በአግባቡ እንዲሰበስብና በትክክለኛ ገበያ እንዲሸጥ ጽሕፈት ቤቱ ከጎኑ ይሆናል፡፡ በዚህ መልኩ ሲሰራም ነው ዘንድሮ በዞኑ ሊሰበሰብ የታቀደው ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ሊሳካ የሚችለው፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የብሄራዊ ጥራጥሬ ምርምር ብሔራዊ አስተባባሪና ተመራማሪ ዶክተር ብርሃኑ አምሳሉ በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ ለረዥም ዓመት ለውጭ ገበያ ሲቀርብ የነበረውን አዋሽ አንድ ዝርያ የሚተካ አዋሽ ሁለት የተዋወቀበት፣ በተመሳሳይ ናስር የሚባለውን ቀይ ቦሎቄ በሴሪ 119 ለመተካት የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል፡፡ ቦሎቄን ከበቆሎ ጋር በማሰባጠር የማምረት ዘዴንና ይሄም ያለውን ጠቀሜታ የማስገንዘብ፤ በአነስተኛ የእርሻ ድግግሞሽ እርሻ የአፈርን ለምነትና እርጥበትን በጠበቀ መልኩ የሚከናወን ግብርናን በእለቱ በተካሄደው ጉብኝት እንዲገነዘቡ ተደርጓል፡፡

እንደ ዶክተር ብርሃኑ ገለጻ፤ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በርካታ ፋይዳ ያላቸው ሲሆን፤ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ፣ እንዲሁም ለድርቅ ተጋላጭነትን ከመቀነስ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽዖ አላቸው፡፡ የአርሶ አደሩ አሁን የተዋወቁት ቦሎቄዎች ከቀደሙት ቢያንስ የ30 በመቶ የምርታማነት ብልጫ አላቸው፡፡ የበሽታ ተጋላጭነታቸው አነስተኛ ነው፡፡ ድርቅን የመቋቋም አቅምም አላቸው፡፡ ሆኖም የዘር ቀለም ልዩነት የላቸውም፡፡ ምክንያቱም በተመሳሳይ ቀለምና መጠን የተሻለ ምርታማነትን ማምጣትን እንጂ የተለየ ዝርያ በተለየ ቀለምና መጠን በማቅረብ የገበያ ክፍተት መፍጠር አይደለም፡፡ ለምሳሌ ትንሿን ነጭ ቦሎቄ ወደውጭ በመላክ በዓመት ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ እየተገኘ ነው፤ ስለዚህ ዝርያው ተለወጠ ማለት ይሄን ገበያ ማጣት ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ በቀይ ቦሎቄ ያለውን ገበያ ማጣት ስለማይፈለግ የምርታማነት ስራው ገበያውን ያማከለ ነው፡፡

ዶክተር ብርሃኑ እንደሚናገሩት፤ የቦሎቄ ዝርያዎቹን አርሷደሩ እንዲጠቀም ከማድረግ አኳያም ለምሳሌ ቀይ ቦሎቄን ወደ ደቡብ ክልል በስፋት የተላከ ሲሆን፤ በሰርቶ ማሳያ ጭምር እንዲያዩት በመደረጉ አምርተው እየተጠቀሙ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ አዋሽ ሁለትም ለዘር አምራቾች ስለተሰጠ፤ በቀጣይ ዓመት በተለይ በመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ላይ አዋሽ አንድን ይተካል የሚል እምነት አለ፡፡ አሁንም በምርምር ላይ ያሉ ዝርያዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ ነቀዝን የሚቋቋሙ ዝርያዎችን የመልቀቅ ሀሳብ አለ፡፡ ከአሁኖቹ በመጠን የሚለዩ ነጭና ቀይ ቦሎቄዎችን፤ እንዲሁም ጥቁርና ዥንጉርጉር ቦሎቄዎችን ለመልቀቅ በሂደት ላይ ነው፡፡ እነዚህ ደግሞ ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር የገበያ ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችሉ ናቸው፡፡

በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የሰብል ልማት ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ በጉብኝቱ በቆሎንና ቦሎቄን አሰባጥሮ በመዝራት የተጀመሩ ስራዎችን አርሶ አደሩ እንዴት እየተገበራቸው እንደሆነና በአርሶ አደር ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ምን አይነት ጅምር ስራዎች አሉ የሚለውን መመልከት ችለዋል፡፡ በዚህም የአርሶ አደሩን ጥሩ ጅምር ስራዎችና ያሉባቸውን ችግሮችም መገንዘብ ችለዋል፡፡ ይህ በጥቂት አርሶ አደሮች ላይ የሚሰራ ፓይለት ፕሮጀክት እንደመሆኑም ውጤታማነቱ እየታየ ወደሌሎች አርሶ አደሮች እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ ሆኖም አሁን ያለው የማባዛት ስራ በቂ ነው ባይባልም አንድ ቴክኖሎጂ በየማዕከላቱ በምርምር ውጤታማነቱ ከተረጋገጠ በኋላ እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በአርሶአአደር ማሳ እና ማሰልጠኛዎች የማላመድና የማስተዋወቅ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡ ከምርምርና ኤክስቴንሽን አካላትም የተቀናጀ ፎረም ስላለ በየደረጃውና በየጊዜው በመገናኘት ሁሉም የራሱን ስራ ይሰራል፡፡

 

ወንድወሰን ሽመልስ

 

 

Published in ኢኮኖሚ

በአሜሪካና ሰሜን ኮሪያ ያለው ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት በተለይ ሰሜን ኮሪያ በተደጋጋሚ የሚሳኤል ሙከራ ማድረጓን ተከትሎ አሜሪካ የአጸፋ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች የሚለው ስጋት ማየሉን የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ አሜሪካ የሰሜን ኮሪያን የሚሳኤል ጥቃት ለመመከት የምትወስደው እርምጃ በሩሲያ ላይ ጫና እንዳለው ይነገራል፡፡ ይህንንም በሩሲያ ሩቅ ምስራቅ ግዛት ጥቃት እንደመፈጸም ነው በማለት ይተነትናሉ።

እንደ ተንታኞች ገለጻ፤ ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ አህጉር ተሻጋሪ የባሊስቲክ ሚሳኤል ሙከራ እያደረገች ነው። በአሜሪካ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ከፈጸመች የአገሪቱ አጸፋ የሚሆነው የመካከለኛ ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ዒላማውን ስቶ በሩሲያ ምድር ሊያርፍ ይችላል።

በአሜሪካ በትጥቅ ቁጥጥር ሕብረት የትጥቅ ማስፈታትና የጉዳት ቅነሳ ፖሊሲ ዳይሬክተር ኪንግስቶን ሬይፍ፣ ከአሜሪካ አላስካ ግዛት የሚተኮሰው ሚሳኤል ዒላማውን ከሳተ በሩሲያ የመሬት ክልል ውስጥ ስለሚገባ በሀገሪቱ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ የማስተካከያ እርምጃዎች ካልተበጁለት ይህን መሰል እንቅስቃሴ የከፋ ችግር ሊያስከትልም ይችላል ይላሉ።

በምስራቅ እስያ የኒውኩለር መቆጣጠር ፕሮግራም ዳይሬክተር ጀፍሬይ ሉዊስ በበኩላቸው፣ አሜሪካ ከሩሲያ ጋር በጉዳዩ በግልጽ መወያየት እንዳለባት ይጠቁማሉ፡፡ የችግሩ ስጋት ያስፈራቸው በሩሲያና ዩሮ እስያ የዓለም አቀፍና ስትራቴጂያዊ ጥናቶች ማዕከል ፕሮግራም ዳይሬክተር ኦሊያ ኦሊከር በጉዳዩ ላይ ከሞስኮ ባለስልጣናት ጋር መምከር እንዳለባቸውና ለመፍትሔውም መንቀሳቀስ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

ናሽናል ኢንተረስት ድረ-ገጽ በትንታኔ ዘገባው እንዳመለከተው፤ አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ የሚተኮሰ ባሊስቲክ ሚሳኤልን ማምከን የሚያስችል መሳሪያ ያላት ቢሆንም መሳሪያው አጋጣሚ ዒላማውን የሚስት ከሆነ ግን በሩሲያ መሬት ስለሚያርፍና በቀጣናው ጉዳት ስለሚያስከትል አሜሪካና ሩሲያ ወደ ጠብ ሊያስገባቸው፤ ሌላ ውዝግብ ሊፈጥር ይችላል፡፡ በጉዳዩ ላይ የተለያዩ አስተያየት እየወጡ መሆናቸው የሚታወቅ ሆኖ በአጠቃላይ የአሜሪካ የፀረ ኒኩሌር ተግባር በአሜሪካና ሩሲያ አደጋ የሚያስከትል መሆኑን ይጠቁማሉ።

ከአሜሪካዋ ግዛት ሃዋይ የሚለቀቀው የመከላከያ ሚሳኤል በሰፊ ቦታ ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ዋሽንግተንን ዒላማ ያደረገን ጥቃት ለመከላከል በሩሲያ አየር ክልል ማለፍ የግድ ይላል፡፡ በዚህ መሰረትም በሩሲያ ሰማይ በኩል ለሚደረገው የሚሳኤል ጥቃት ከለላ ሲሰጥ አደጋ ይፈጠራል የሚል ስጋት ያጭራል።

ይብዛ ይነስ ጥቃቱን ለመከላከል ከአላስካ የሚደረገው እንቅስቃሴ አቅጣጫውን በመቀየር ከሩሲያ ውጭ ቢሆን ተመራጭ ነው፡፡ ለሚደረገው የአቅጣጫ ቅያሳም በጣም ጥንቃቄ የሚሻ መሆኑ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል የሩሲያ ቅድመ ማስጠንቀቂያ የፀረ ሚሳኤል ጥቃት ከአላስካ ሲጀመር የማንቂያ ደወል የሚሰጥ ሲሆን፤ በሩሲያውያን ፍልስፍና የመጀመሪያው ጥፋት አጸፋዊ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ መቀበል መሆኑም የሚናገሩ አልታጡም፡፡

አሁንም በግልጽ የሚያመላክቱ ትክክለኛ መረጃ ባይኖርም ከሩሲያ ታሪካዊ ሁኔታ በመነሳት በተጨማሪ ነገሮች ሊታዩ፣ ማንም ሊጠብቀው ወይም ሊቆጣጠረው የማይችል ነገር ሊከሰት ይችላል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሰዎች የመሰላቸውን ሊናገሩ ይችላሉ፤ በተግባር የሚሆነው ግን ማንም ያልጠበቀው ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡ ለዚህም ስለሚሆነው ነገር አሁን በእርግጠኝነት መልስ መስጠት እንደማይቻል የሚናገሩም አሉ፡፡

ነገር ግን ሩሲያውያን የአሜሪካ የሚሳኤል አምካኝ በመሬታቸው ማረፍ ብዙም ባያሳስባቸውም፤ የሞስኮው አስተዳደር ግን የሚሳኤል አምካኝ የሩሲያ ባሊስትክ ሚሳይል ለማስጀመር ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሊሆን እንደሚችል ሊመክሩበት እንደሚገባ አንድ አንድ ተንታኞች ያመለክታሉ፡፡

በርካታ የህዝብ ብዛት ያለበት የሩሲያ ሩቅ ምስራቅ የመደብደብ አጋጣሚው በጣም ትንሽ ቢሆንም፤ በቅድመ ባሊስቲክ ሚሳይል ማስጠንቀቅያ ጉዳይ ላይ ሊመክሩበትና የመረጃ መለዋወጥ ዘዴ መቀየስ እንዳለባቸው በሞስኮ ከፍተኛ የኢኮኖሚክስ ትምህርት የአውሮፓና ዓለም አቀፍ ጥናት ተመራማሪ ቫሲሊይ ካሺን ይመክራሉ፡፡

ምንም እንኳ በግልጽ የታወቀ ነገር ባይኖርም በተለይ በአሜሪካ በኩል ከመሬት በሚነሳ የሚሳይል ማምከን ጋር በተያያዘ የተሰጠ ነገር እካሁን የለም። ይሁነና ሩሲያውያን እንደጠቃሚ ነገር ሊያዩት እንደሚገባ ተንታኞቹ ይጠቅሳሉ፡፡ አሜሪካ በባሊስቲክ ሚሳይል አምካኙ ባልፈለጉት ቦታ ራሱን በራሱ እየፈራረሰ ጉዳት ማድረስ የሚያስችለው መሳሪያ አለመግጠማቸውንም እንደምክንያት ያነሳሉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ አንድ ተንታኞች ራሱን በራሱ የሚያፈነዳ መሳሪያ እንዳልተገጠመለት ቢገልጹም፤ ያለ ሚሳይል የሚንቀሳቀሱ ተሸከርካሪ ዎችም ቢሆን ሊያጠፋቸው እንደሚችል የሚገልጹም አልጠፉም፡፡ በአሜሪካና ሩሲያ መካከል አማካሪ አካል ቢመቻችም የራስ በራስ ማጥፋት ዘዴው ጥቅም ላይ ለማዋል በቂ ጊዜ የመኖሩ ጉዳይ ግን ጥያቄ ማንሳቱ አልቀረም፡፡ እንደውም አንድ አንድ ተንታኞች በቂ ጊዜ እንደሌለው ይገልጻሉ፡፡

የሚሳይል መከላከል ተግባር በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የሚከሰት ነው፤ ፕሬዚደንቱም ቢሆኑ እስከሚከሰት ድረስ ሊያውቁት አይችሉም፤ በማለት ምክንያታቸው ይጠቅሳሉ፡፡ በመጨረሻ ላይ አሜሪካና ሩሲያ በጸረ ሚሳይሉ ጉዳይ ላይ በመምከር የተስማሙ ቢሆንም፤ አሜሪካ በሩሲያ የቅድመ ማስጠንቀቅያ በትክክል መፈጸም ማመን እንዳለባትና ያልታሰበ የኒኩሌር ጦርነትን መቆጣጠር እንዳለበት ናሽናል ኢንተረስት ድረገጽ አስታውቋል፡፡

 

በሪሁን ፍትዊ

 

 

Published in ዓለም አቀፍ

 

መንግሥት ለአምራቹ ኃይል የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማመቻቸት የጥቃቅንና አነስተኛ አደረጃጀትን በማዋቀር አቅማቸውን ለማሻሻል ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በአፍሪካ በተለይ በኢትዮጵያ የሥራ አጥ መጠኑ ከዕለት ተዕለት እያሻቀበ በመሆኑ መንግሥትም የሥራ ዕድል ለማስፋፋት ስልትና ስትራቴጂ ሲነደፍ መታየቱ የተለመደ ሆኗል፡፡

ወጣቱ ማህበረሰብ በከፍተኛ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ተመርቀው ሲወጡ በበቂ ሁኔታ በመንግሥት ሆነ በግሉ ዘርፍ የሥራ ዕድል ባለመመቻቸቱ የማይናቅ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል ሥራ አጥ ነው፡፡ የሀገሪቱ ገቢ ቢያድግም ቅሉ በጀቱን በአግባቡ ለወጣቱ ማህበረሰብ ለውጥ ማዋሉ ላይ ብዙም የተኬደበት አይመስልም፡፡

በአመዛኙ የሀገሪቱ በጀት ለመሰረተ ልማት (infrastructural development) ፈሰስ በመደረጉ የወጣቱን ሁለተናዊ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ተግባር በበቂ ሁኔታ አልተሰራም፡፡ በመሆኑም በተለይ ወጣቱ አልፎ አልፎ ለጥፋት ኃይሎች እኩይ አላማ ማስፈፀሚያ የሚሆንበት አጋጣሚ እየተፈጠረ ነው።

መንግሥት በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች ወጣቱን በማደራጅት ውሎ የሚገቡበትን የሥራ መስክ እየነደፈ የቀጣይ ህይወታቸውን ትልም ይቀይሳል፡፡ በገጠሪቷ ክልል አፍላ ጉልበት ያላቸውን አካላት እንዲደራጅ በማድረግ በግብርና ማኑፋክቸሪንግ እና በሸቀጣ ሸቀጥ መሸጫ መስኮች ተሰማርተው ከራሳቸው አልፎ--ተርፎ የሀገሪቷ ዕድገት አውታር ይሆኑ ዘንድ ተጨባጭ ክንውኖችን ሲከውኑ ይታያል፡፡ ሆኖም በከተማ ለሚኖረው የነብር ጣት የሆነውን ወጣቱን ትውልድ በማኑፋክቸሪንግ፣ በሸቀጣ ሸቀጥ መሸጫ ሱቆች፣ ማስታወቂያ፣ ህትመት እና በሌሎችም የሥራ ዘርፎች እንዲሰማሩ በማድረግ ከድህነት አረንቋ የሚወጡበትን መደላድል ሲያመቻቸ ይታያል፡፡

በነዚህ ዘርፎች መንግሥት ወጣቱን ሲያደራጅ የሀገሪቷን ግብአት አቅም ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ የሰው ኃይል ምጣኔ ሀብትና መሬት ይዞታን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በሌሎች የሥራ መስኮች መንግሥት ማሰማራት ሲቻል ጥረት አለማድረጉ ሰፊ ክፍተት ፈጥሯል የሚል እሳቤ አለኝ፡፡

መንግሥት ወጣቱን በነዚያ ዘርፎች ሲያደራጅ እርግጥ የሌሎች ሀገራትን ልምድና ተሞክሮ በመቀመር ነው፡፡ የወጣት ወገኞቻቸውን ፍላጎት ለማርካት አያሌ የሥራ ፈጠራ መስኮች ፈጥረው የብልፅግና ማማ ላይ የደረሱ ሀገራት አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ቻይና፣ ሲንጋፖር፣ ህንድ፣ ኢንዶኒዥያ፣ ባንግላዲሽ ፣ጃፓንና ማሌዥያ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እነዚህ ሀገራት ስፍር ቁጥር በሌላቸው የሥራ መስኮች ትውልድን በማሳተፍ ማህበራዊ ዋስትናን በተወሰነ መልኩ ሊያረጋግጡ ችለዋል።

በቴክኖሎጂ ፈጠራ (innovation) በግብርና፣ ቢዝነስ፣ በቁጠባና ብድር፣ ባንክ፣ በቱሪዝም ዘርፍ፣ በሸክላ ሥራ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በምግብና መጠጥ ዝግጅት፣ ትምህርት፣ ስልጠናና በሌሎችም ተጓዳኝ የሥራ ዘርፎች የወጣቱን ዕውቀትና ጉልበት ብሎም የተነሳሽነት መንፈስን እንደ አንድ እምቅ ሀብት በመቁጠር ተጨባጭ ለውጥ እንዲያስመዘግቡ አግዟቸዋል፡፡ ወጣቱን በአያሌ ሥራዎች በማኖር የሥራ አጥ መጠኑን ቁልቁል እንዲንወርድ አድርገውታል፡፡ በሀገራችን ግን በተዘረዘሩት መስኮች ማሰማራቱ ላይ ሲታቀድም ብዙም አይታይም፡፡ ይልቁንስ ጭብጥ በማትሞላ የሥራ ፈጠራ ዓይነቶች ዕውቀታቸውን ጉልበታቸውን ይዘው ለሚወጡ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች እንቅፋት የሚሆኑ መንግሥታዊ አካላት በየመዋቅሩ ከመኖራቸው ጋር ተደምሮ የሥራ ፈጠራው ሥራ ከችግሩ አንፃር ሲታይ ብዙ የሚቀረው እንዳለ መታወቅ ተገቢ ነው።

ከድህነት በታች ወለል የሚገኘውን ትውልድ ለመታደግ ከተፈለገ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ማሰማራቱ የሚያስገኘው ትሩፋት የትየለሌ ሊሆን እንደሚችል ግልፅ ነው፡፡ ቀደም ሲል የገለፅናቸው ሀገራትም በአያሌ የሥራ ዘርፎች ወጣቱን በማነቃነቃቸው ማህበራዊ እሴቶቻቸውንና ሰላማቸውን ማስጠበቅ ችለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከሌሎች ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆኑና አዳጊ ሀገራት ተብለው ስማቸው በዓለም መድረክ እንዲጠራ ድጋፍ ሆኗቸዋል፡፡

በውስን የሥራ መስኮች ማሰማራቱ እንደ አሸን የፈላውን የሥራ አጥ ቁጥሩን 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ በጀት መያዙ ብቻ ችግሩ ሊቀረፍ ይችላል ብሎ መታሰብ የለበትም ፡፡ መታየት ያለበት እንደ ተራራ የተከመረውን ችግር ለመቅረፍ የበጀት ምደባ ብቻ ሳይሆን በምርመራና ጥናት ተደግፎ ወጣቱን በሌሎች አዲስ የሥራ መስኮች ማሰማራቱ ላይ ነው ትልቁ ቁም ነገር የሚመስለኝ፡፡

 

በመሐሪ በየነ

 

 

Published in አጀንዳ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።