Items filtered by date: Monday, 09 October 2017

የዳርት ስፖርት በሁለት ጣት በምትያዝ ሚሳኤል መሰል ጦር በግድግዳ ላይ በሚሰቀል ክብ ቦርድ ላይ ኢላማ በማነጣጠር እና በመወርወር የሚደረግ ስፖርታዊ ጨዋታ ነው። አጨዋወቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እና በዓለም አቀፍ ስፖርት የተመዘገበ ሲሆን «ዳርት» የራሱ ህጎች ያሉት እና ተጫዋቾች በሚያስቆጥሩት ነጥብ መሰረት አሸናፊው የሚለይበት ነው።

ዓለም አቀፍ እውቅና ኖሮት ስፖርታዊ ውድድሮች ቢዘጋጅለትም ይህ ጨዋታ በባህላዊ ስፖርት ውድድር የተመዘገበ ነው። የዳርት ስፖርት ለዘመናት በታላቋ ብሪታንያ እና በአየርላንድ ውስጥ ተወዳጅ ሆኖ እስካሁንም ድረስ መዝለቅ የቻለ ነው። ከዚህም ሌላ በኔዘርላንድ፣ጀርመን፣ በስካንዴኔቪያ እንዲሁም በአሜሪካ ተወዳጅነትን አትርፎ የተስፋፋ የስፖርት ዓይነት ነው።

የዳርት ጨዋታ በድሮ ዘመናት በጦር ግንባሮች አካባቢ በስፋት የሚጫወቱት ተወዳጅ ባህላዊ ስፖርት ነው። በተለይ በአንደኛው የዓለም ጦርነት አካባቢ አልሞ ተኳሽ ወታደሮች ኢላማ ለመለማመድ እና እራሳቸውን ዘና ለማድረግ ይጠቀሙበት ነበር። በዚህም ስፖርቱ በስፋት እውቅናን እያተረፈ እና ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን እያገኘ ሊመጣ ችሏል። ሌላኛው የዳርት መጫወቻ ቦርድ ከክብ እና ጠንካራ ጣውላ የሚሰራ ሲሆን፣ በተለያዩ ቀለማት የኢላማ መድረሻ ነጥቦች ተስሎበታል። ለመጫወቻ ምቹ ተደርጎ በግርግዳ ላይ ይሰቀላል። ተወዳዳሪዎቹም ከትንሽ ፕላስቲክ ወይም እንጨት ጫፏ ላይ የሾለች መጫወቻ ይይዙና ነጥብ ለማስቆጠር በየተራ ፉክክር ያደርጋሉ።

በኢትዮጵያ ውስጥም ይህ ስፖርት መዘውተር ከጀመረ ዋል አደር ብሏል። ሆኖም ግን ስፖርቱ በሚፈለገው መጠን አድጓል የሚባል ደረጃ ላይ አልደረሰም። ሆኖም እንደ አንድ ስፖርታዊ ውድድር እውቅና ማግኘቱና ዕድገት እንዲያሳይ ጥረት የሚያደርጉ ወገኖች መኖራቸው ይበል የሚያሰኝ ጅምር ነው።

የዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን አባል የሆነው የኢትዮጵያ ዳርት ፌዴሬሽን ባለፈው ቅዳሜ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂዷል። በዚህ የውይይት መድረክ በበጀት ዓመቱ ያከናወናቸው ተግባራት በርካታ ችግሮች የተደራረቡበት እንደነበር ተገልጿል። ፌዴሬሽኑ በገንዘብ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ እየተፈተነ መሆኑና ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት አለማግኘት ከባድ ፈተና ውስጥ መግባቱ ተገልጿል። በሌላ ጎኑ ደግሞ በክልሎች እና በተለያየ ደረጃ ያሉ አካላት ስፖርቱን ለማስፋፋት ላደረጉት ጥረት አድናቆት ተችሮታል።

ፌዴሬሽኑ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን ባካሄደበት ወቅት የኢትዮጵያ ዳርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ጎይቴ እንደሚሉት፤ ሰሞኑን በጃፓን አገር እየተካሄደ ባለው የዳርት ዓለም አቀፍ ሻምፒዮና ውድድር ላይ ለመሳተፍ ኢትዮጵያ ተጋብዛ ነበር። ፌዴሬሽኑ በተለያዩ ወቅቶች ከዓለም አቀፍ ውድድር አዘጋጆች ጋር በመፃፃፍ እና ተግባቦት በመፍጠር በውድድሩ ለመሳተፍ ጥረት እያደረገ ነበር፡፡ በዝግጅት ደረጃም ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡ ይሁንና በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከስፖንሰሮች ለጉዞ ለሚያስፈልገው በጀት ድጋፍ ባለማድረጋቸው በውድድሩ ላይ ሳይሳተፍ መቅረቱን ነው የገለፁት። ከዳርት ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ ኢትዮጵያን ወክሎ የተገኘ ኃላፊ አለመኖሩንም ጠቁመዋል። በአጠቃላይ በ2009 በጀት ዓመት ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እጥረት እንደገጠመው አስገንዝበዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፤ መንግሥት ለፌዴሬሽኑ ከሚደጉመው ውስን በጀት በስተቀር ለአገሪቱ የዳርት ስፖርት ማሳደጊያ ምንም ተጨማሪ የፋይናንስ ምንጭ ስለሌለ እና የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ ማግኘት ባለመቻሉ ሥራውንም በታሰበው ልክ ለመስራት እክል እንደፈጠረ ነው ያስገነዘቡት። ፌዴሬሽኑ በ2009 .ም በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የዳርት ስፖርት እንዲስፋፋና ጠንክሮ እንዲወጣ የተቻለውን ያክል ጥረት ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም፤ በበጀት ዓመቱ በተካሄደው አገር አቀፍ ሻምፒዮና የተሳታፊዎች ቡድን ከስምንት ሊበልጥ አልቻለም።

ይሁንና ፌዴሬሽኑ በበጀት ዓመቱ ለሥራ አመቺ የሆኑ ንድፈ ሃሳቦችን ተግባራዊ አድርጓል፡፡ ሥራዎችም በጥራት እንዲከናወኑ የተቻለውን ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም አስረድተዋል። «ለስፖንሰር ሺፕ ያላንኳኳው በር የለም» ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ እስካሁን የተደረጉት ጥረቶች ባይሳኩም በቀጣይ የበርካታ ተቋማትን ደጅ መጥናቱንና የማሳመን ሥራውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል። በአሁኑ ወቅት ባለው ሂደት ለስፖርቱ አጋር አካላት ማፈላለጉ አዋጭ ባለመሆኑ በ2010 አዲስ ስልት መንደፉንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዳርት ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን አላምረው በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ ፌዴሬሽኑ በርካታ ውጣ ውረዶችን ያለፈ መሆኑን ተናግረዋል። በዚያው ልክ ደግሞ ቀደም ካሉት ዓመታት አኳያ የተሻለ አፈፃፀም እና ጥረት እየተደረገ ነው። በበጀት ዓመቱ በርካታ ድርጅቶችንም ለስፖርቱ ድጋፍ እንዲያደርጉ ደጅ መጥናታቸውን ጠቁመው፤ አንዳቸውም ድርጅት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ አስገንዝበዋል። ሌሎች ፌዴሬሽኖችም የገንዘብ አቅማቸውን ያጎለበቱበት ልምድ እና ተሞክሮ በመቅሰም በቀጣይ የተሻለ ተግባራት ለማከናወን ጥረት በመደረግ ላይ እንደሆነ ነው የተናገሩት።

ይህ እንዳለ ሆኖ ፌዴሬሽኑ አያሌ አበረታች ተግባራትንም ማከናወኑን ይገልፃሉ። በበጀት ዓመቱ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ከሁሉም ክልል እና ሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች ለተውጣጡ 21 ወንዶች እና 27 ሴቶች የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል። ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀትም በወልቂጤ፤ በቡታጅራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለ56 ሰልጣኞች የአሰልጣኝ ስልጠና መስጠቱን አስታውሰዋል። ፌዴሬሽኑ የግንኙነት አድማሱን ከማስፋት አኳያም ከዓለም አቀፍ እና የአፍሪካ ዳርት ፌዴሬሽን እንዲሁም በአገር ውስጥ ካሉ ሚኒስቴሮች እና የክልል ተቋማት ጋር የትውውቅ አድማሱን እያሰፋ መሆኑን አውስተዋል።

የፌዴሬሽኑን ዓመታዊ ኦዲት ያቀረቡት ወይዘሮ የክቴ አሰፋ በበኩላቸው፤ ለፌዴሬሽኑ ንብረት ሲገዛ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ተገዝቶ ገቢ ሲደረግ በትክክለኛው አካሄድ አለመከተሉ፣ በዓመቱ መጨረሻ ቆጠራ መካሄድ ሲገባው ሰኔ 2009 .ም አለመካሄዱ አግባብ እንዳልሆነ ይናገራሉ። በመንግሥት አሠራር ሁሌም የዓመቱ መጨረሻ ቆጠራ መካሄድ እንዳለበት በማሳሰብ። ፌዴሬሽኑ ሁለት አካውንት ያለው ሲሆን በአንደኛው አካውንት ሂሳቡ የተወራረደ ሲሆን፤ ሌላኛ ደግሞ ጉድለት አሳይቷል። ይህም በውስጥ የኦዲት ባለሙያዎች እንዲስተካከል መደረጉን ገልፀው፤ የፋይናንስ አሰራርኑ በሚገባ እንዲከተልም አሳስበዋል።

በጉባዔው ላይ የተገኙት የክልል ተወካዮች በበኩላቸው፤ ፌዴሬሽኑ ፕሮጀክቶች እንዲበራከቱ፣ አጋር አካላት ስፖርቱን እንዲደግፉ የተጀመሩት ጥረቶች በጣም አነስተኛ በመሆናቸው አጽንኦት በመስጠት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል። በአደረጃጀት ረገድም ብዙ ተግባራት በተፈለገው ደረጃ አልተከናወኑም። ለአሰልጣኞች ብቻ ሳይሆን ለዳርት ስፖርት ዳኞችም በበጀት ዓመቱ ስልጠና አለመሰጠቱ አግባብ እንዳልሆነ አስያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።

ለስፖርቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እጥረትም ሌላው ፈታኝ ጉዳይ በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ሊያስብበት ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል። በሌላ ጎኑ ደግሞ ስፖርቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት የወጠናቸው ሃሳቦች እና በቅርቡ ለመጀመር ያቀዳቸው ሃሳቦች አበረታች እንደሆኑ በመጠቆም ቅንጅታዊ ሥራም እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ዳርት ፌዴሬሽን ከሁለት ዓመት በፊት የዓለም አቀፍ ዳርት ፌዴሬሽ አባል መሆኑ ይታወቃል። ይህም ከአፍሪካ በዓለም አቀፉ ፌዴሬሽ አባል ከሆኑ አምስት ቀዳሚ አገራት አንዱ ነው። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ከመንግሥት የሚደረግለት ዓመታዊ ድጋፍ ከ225ሺ ብር የዘለለ አለመሆኑ የስፖርቱን ዕድገት አዝጋሚ አድርጎታል።

 

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

Published in ስፖርት

በዓለም አቀፍ ደረጃ የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ተወዳጅነትን እያተረፈ የመጣ ስፖርት ከሆነ ሰነባብቷል። በርከት ያሉ ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችም በዚሁ ስፖርት ላይ ይካሄዳሉ። አካል ጉዳተኞችን የሚያሳትፈው ይህ ስፖርት ከባድ የሚመስሉ ነገሮች ሁሉ ጠንክረው ከሰሩ ተግባራዊ ለማድረግ እንደማይከብዱ ለማሳየት ምሳሌ ከሚሆኑ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ይመደባል። በአገራችንም አካል ጉዳተኞችን በቅርጫት ኳስ ላይ ለማሳተፍ ጉልህ ባይሆንም ጅምር ሙከራዎች ይታያሉ። ስፖርቱን የማስረፅ እና የማሳደግ እሳቤው ያልዳበረ በመሆኑም በርካታ ፈተናዎች እንደሚገጥሙት በስፖርቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የዝግጅት ክፍላችን «የዊልቸር ቅርጫት ኳስን» በተመለከተ ሰሞኑን በተካሄደ የባለሙያዎች ስልጠና ላይ ተገኝቶ ነበር። የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመተባበር ለዊልቸር ቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ ዳኞች እና የጉዳት ዓይነት መዳቢዎች (ክላሲፋየሮች) ኢንተርናሽናል ስልጠና ሰጥቷል። በስልጠናው ላይ 69 ወንዶች እና 21 ሴቶች በድምሩ 90 የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ስፖርት ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል። በዚህም በስፖርቱ ላይ እየታዩ ያሉ መልካም ውጤቶች እንዲሁም ፈተናዎች ምንድን ናቸው? የሚለውን ለማወቅ ተሳታፊዎቹን አነጋግረን ከዚህ እንደሚከተለው ለመዳሰስ ሞክረናል።

አቶ ፍሬ አሰፋ የዊልቸር ቅርጫት ኳስ አሰልጣኝ ነው። የአሰልጣኝነት ሙያን ከሃሮማያ ወስዷል። የከዚህ ቀደሙ ስልጠና በልምድ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን በመግለጽ በዚህኛው ስልጠና ሥነ ልቦና ላይ ያተኮረ ሰፊ ልምድ እንዳገኘ ይናገራል፡፡ አዳዲስ ስፖርተኞችን በምን መልክ መቅረፅ እንደሚቻል ቴክኒካል እውቀት መማሩን ይገልጻል።

«በዚህ ወቅት ለአካል ጉዳተኞች የተሰጠው ትኩረት አናሳ ነው። ሆኖም ችግሩን ለመቅረፍ ጅምር ሙከራ እንዳለ ማስተዋል ይቻላል» በማለትም፤ በማንኛውም ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሰው ፍላጎት ካለው በስፖርቱ ላይ ተሳታፊና ውጤታማ መሆን ይችላል በማለት ይገልፃል። በማህበረሰቡ እና በስፖርት ቤተሰቡ ላይ ያለውን የአመለካከት ችግሩን መቅረፍ እንደሚገባም ይናገራል። ለዚህ ደግሞ ይህን መሰል ስልጠና በተደጋጋሚ አጠናክሮ መስጠት ያስፈልጋል ይላል።

«ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ወደ ስፖርቱ ማካተት መጀመሩ የሚበረታታ ቢሆንም ከዚህ በበለጠ ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል» የሚል አስተያየቱን የሚሰጠው አሰልጣኝ ፍሬው፤ ስፖርቱን የሚያግዙ ግብዓቶች እጥረት ሊቀረፍ ይገባል ይላል። በስፖርቱ የሚታዩ ተግዳሮቶች እንዳሉ በመጥቀስ፤ በተለይ ልምምድ ለመስራት ኳስ እና መጫወቻ ሜዳ ቢኖርም እንኳን «ዊልቸሩን» በቀላሉ ማግኘት እንደማይቻል ያስረዳል። የልምምድ እና የውድድር ጀምናዚዬም እጥረት በራሱ ሊፈቱ ከሚገቡ ችግሮች መካከል መሆኑን ይጠቅሳል።

ድንቅነሽ አውደው የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ስፖርተኛ ነች። ከዚህ ቀደም በተለምዶ የዓለም አቀፍ የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ህግ እውቀት ሳይኖራቸው ይጫወቱ እንደነበር ትናገራለች። አሁን ላይ ግን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና ወስደዋል። ለስፖርቱ ፍቅር ቢኖራቸውም በየቤቱ የቀሩ አካል ጉዳተኞች አሉ። የራሱ ፌዴሬሽን እና ውድድር አለመኖር በራሱ ችግር ነው፡፡ በበቂ ሁኔታ ዊልቸር አለመኖሩም ሌላኛው የስፖርቱ ዕድገት እንቅፋት መሆኑን ታስረዳለች።

«ቀይ መስቀል ዊልቸር በተወሰነ መልኩ ያቀርባል። ሆኖም በቂ አይደለም። ስፖርቱ ዓለም አቀፍ ቢሆንም አሁንም በሀገራችን ደካማ እንቅስቃሴ ነው ያለው» በማለት በአንፃራዊነት በያዝነው ዓመት ላይ ስፖርቱን ለማነቃቃት እየተደረገ ያለው ጅምር ሙከራ መልካም መሆኑን ትናገራለች። ክለቦች እና ፌዴሬሽኑ በተጠናከረ ሁኔታ ተደራጅተው ቋሚ ውድድሮች ቢዘጋጁ ውጤቱ አመርቂ እንደሚሆን ትገልፃለች። ይህን መሰል የብቃት ማሳደጊያ ስልጠና በተደጋጋሚ ተጠናክሮ መዘጋጀት ይኖርበታል የሚል ሀሳብ አላት። ሰሞኑን የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር በጀት ይዞ የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን እንዲያቋቁም በጋራ ለመጠየቅ ማሰባቸውንም ትናገራለች። ስፖርቱን ለመቀላቀል የሚፈለጉ አካል ጉዳተኞች በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች ቢኖሩም እንቅስቃሴው ግን በተወሰኑ ክልሎች ብቻ መኖሩን ተገቢ አለመሆኑንም ታስረዳለች።

በስልጠናው ላይ የስፖርቱ ዳኞች ተሳታፊ መሆናቸው በጎ ጅምር መሆኑን የምትናገረው ድንቅነሽ «የዳኝነት ስልጠናም ቢጠናከር ውድድሮችን በበቂ ሁኔታ መምራት ይቻላል» ትላለች። በሳምንት ሦስት እና አራት ቀናት ስፖርቱ ቢሰራ በጣም ማደግ እንደሚችል ነው በሙሉ የራስ መተማመን አስተያየቷን የምትሰጠው። ሁሉም የስፖርት ቤተሰብ የአካል ጉዳተኞች «ዊልቸር ቅርጫት ኳስ» ለማሳደግ መነሳት ይኖርበታል ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች።

ተሾመ ጫላ ከኦሮሚያ ክልል አሰላ ከተማ የመጣ አሰልጣኝ ነው። ፌዴሬሽኑ ይህንን ፕሮግራም ማዘጋጀቱ በራሱ ቢያስመሰግነውም አሁንም ብዙ እንደሚቀረው ይናገራል። ከዚህ ቀደም ይህን መሰል ስልጠና ቢወስዱም ተከታታይነት ስለሌለው እና በውድድሮች ስላልታገዘ አመርቂ ለውጥ ሊመጣ አለመቻሉን ይገልፃል። የመወዳደሪያ ዊልቸር አንዳንድ ጊዜ በእርዳታ ቢመጣም የመወዳደሪያ ሜዳው ለዕቃው ምቹ ባለመሆኑ ችግር ይገጥማል በማለት፤ ውድድሮችን ለማዘጋጀትም ከባድ እንደሆነ ያስረዳል።

አቶ ተሾመ፤ ፌዴሬሽን ቢኖር ግን የተለያየ ድጋፍ በማፈላለግ ውድድር ማዘጋጀት እንደሚቻል ያስረዳል። በስፖርቱ ተሳታፊ ለመሆን በአካል ጉዳተኛው በኩል ሰፊ ፍላጎት ቢኖርም የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን ይገልፃል። በተለይ የባለሙያ እና የቁሳቁስ እጥረት ፍላጎትን እና ተግባር እንዳይመጣጠኑ ማድረጉን በቁጭት ይገልፃል። አሁን ላይ ስፖርቱን ለማሳደግ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ እንደሆነም ያስረዳል። የመላ ኢትዮጵያ የፓራሊምፒክ ውድድር የተጀመረው በ1999 .ም ቢሆንም በታሰበው ልክ ሊያድግ አለመቻሉንም ይናገራል። ለውጥ ለማምጣት በሙሉ ፍቃደኝነት እና ቁርጠኝነት ከተሰራ የማይቻል ነገር እንደሌለም ያስረዳል።

አሰልጣኝ ተሾመ «የተሰጠን ስልጠና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅ ነው። አፍሪካን ወክለን ብንሳተፍ ከማንም የምናንስ አይመስለኝም፡፡ ብዙ ደክመን ዕድል ካላገኘን አሁንም ዕድሜ መቁጠር ነው። የሚመለከተው አካል ሁሉ በቀናነት ተመልክቶ ዓለም አቀፍ ተሳትፎ እንዲኖር ጥረት ሊያደርግ ይገባል። በዚህ ስልጠና ላይ ያልተሳተፉ ክልሎችም አሉ። በመነጋገር ውድድር ማዘጋጀት ላይ ርብርብ ሊደረግ ይገባል። ወደ ምስራቅ አፍሪካ እንኳን ሄደን የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ የልምድ ልውውጥ ብናደርግ ቀላል አይደለም» በማለት በፍላጎት እና በሙሉ ልብ ስፖርቱን ለማሳደግ አብረን እንስራ የሚል መልዕክቱን ያስተላልፋል።

አቶ አብዱልፈታ ተማም የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው። ስልጠናው በፌዴሬሽኑና በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር መዘጋጀቱን ይናገራሉ። በስልጠናው ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች ያነሷቸው ችግሮች በትክክልም የስፖርቱ ፈተናዎች መሆናቸውንም ይናገራሉ። ስፖርቱ ለሀገራችን አዲስ እንደመሆኑ መጠን ክለብ ለማቋቋም የመጀመሪያ ሥራ መሆን ያለበት ስልጠና መስጠት መሆኑን ይገልፃሉ። ስምንት ክልሎች ላይ ስፖርቱ መኖሩን ጠቁመው እንደዚህ ዓይነት ስልጠናዎች በስፋት መስጠት የሚቻል ከሆነ መልካም ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ይናገራሉ። ፌዴሬሽኑ ራሱን ችሎ እንዲወጣ ግፊት እየተደረገ እና የማቋቋም ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ያስረዳሉ። ስፖርቱ እንዲስፋፋ ባለፉት ሁለት የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ላይ የማስተዋወቅ ሥራ ተሰርቷል። በዚህ ዓመትም የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታ ላይ ውድድር እንዲካሄድ ጥያቄ መቅረቡን ይገልፃሉ።

የፌዴሬሽኑ ባለሙያ የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ውድድር በአካል ጉዳተኞች ቀን እንዲካሄድ መታሰቡን በመግለፅ፤ ስፖርቱ አዲስ ከመሆኑ አንፃር እና አሁንም የቁሳቁስ ችግሮች ፈተና መሆኑን ስፖርተኛውን በቀላሉ ማሳተፍ እንደሚቸግር ይናገራሉ። ስልጠናው እንዳለቀ ተሳታፊዎቹ ወደ ክልላቸው በመመለስ በተመሳሳይ ባልደረቦቻቸውን እንዲያሰለጥኑ እንደሚደረግ አስረድተዋል። በቀጣይ በቂ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ታቅዷል። ተከታታይነት ያላቸው ስልጠናዎች እንደሚሰጡ፣ የቁሳቁስ ችግሩን ለመቅረፍም ትኩረት እንደሚደረግም ገልጸዋል።

 

ቦጋለ አበበ

 

 

Published in ስፖርት
Monday, 09 October 2017 21:33

«ዛላንበሳ ቐረብ ማይ»

የጉዞ ማስታወሻ

ባለፈው ሳምንት ቃል በገባሁት መሰረት በትግራይ ክልል የነበረኝን አስገራሚ ቆይታ ቀጣይ ክፍል ዛሬም ይዤላችሁ ቀረብኩ። ባለፈው ፅሁፌ ለመዳሰስ እንደሞከርኩት የመስቀልን በዓል በዓዲግራት እንዲሁም ስለ ኢሮብ መስቀል ቃኝተናል። ዛሬ ደግሞ ከኢሮብ ወደ አዲግራት በነበረን መልስ ጉዞ ስላጋጠመን ላካፍላችሁ።

ከኢሮብ ማደሪያችን ወደነበረው ዓዲግራት ከተማ ስንመለስ ከተለያየ መገናኛ ብዙሃን ተውጣጥተን ነበርና የሄድነው ለምን ወደ ዛላንበሳ ጎራ ብለን ቡና አንጠጣም የሚል ሀሳብ ቀረበ። ከመካከላችን አንዳችንም ቢሆን አላንገራገርንም ነበር። ኢሮብ ላይ ስላየነው አስገራሚ የመስቀል በዓል አከባበር እንዲሁም ሌሎች ወጎችን እየኮመኮምን መንገዳችንን ወደ ዛላንበሳ አደረግን።

መኪናችን የተመከረ ይመስል ዛላንበሳ እንደደረስን ጎማው ተነፈሰ። በወቅቱ እውነቱን ለመናገር መኪናው ስለመቆሙ ያሳሰበው ሾፌራችን ብቻ ነበር። እኛ ቀልባችን የነበረው ከኤርትራ ጥቂት ኪሎሜትሮች አዋሳኝ ቦታ ላይ እንደቆምን የሚያመላክት ታፔላ አጠገብ ቆም ብለን ምስላችንን ማስቀረት ላይ ነው። ግን ያሰብነው ሳይሳካ ቀረ። ለምን አትሉኝም ልክ እንደኛው ከጥቂት ወራት አስቀድሞ የሀገርን ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥልና አካባቢን ሊያስቃኝ በሚችል መልኩ ፎቶ ተነስተው በማህበራዊ ድረ-ገፅ ባስመለከቱ ግለሰቦች ምክንያት የኬላው ጠባቂ ተጠያቂ እንዲሆን ተደርጓልና እናንተም አትችሉም የሚል ምላሽ ተሰጠን። ታዲያ የዚህ ጊዜ ነው ወደ ዛላምበሳ የመጣንበት ቡና መጠጣት ሀሳብም ሆነ የፎቶ መነሳት ፍላጎታችንን ገታ አድርገን ስለ መኪናችን ያሰብነው።

የተሰጠንን ምላሽ ተቀብለን በመኪናው ቸርኬ ጥቂት ተጓዝን። አሁን የበለጠ ዛላምበሳ ጦርነቱ ምን ያክል እንደጎዳት ለመረዳት ቻልን። አካባቢው እንኳን አይደለም ጦርነት እንደነበር ለሚያውቅ ለማያውቀውም በግራና በቀኝ የቆሙት ፍርስራሽ ግድግዳዎች የዛ ክፉ ጠባሳ አሳባቂዎች ናቸው ። እናም የኋሊት 18 ዓመታትን አስጉዞ ያንን ጊዜ እንድናስብ አደረገን። ከመካከላችን ሰፊ መረጃ የነበረው አንድ ጋዜጠኛ በወቅቱ የነበረውን ነገር ያወጋን ጀመር። ከእርሱ ንግግርና ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ መቃኘት እንደቻልነው ከተማዋ በእነዚህ ጊዜያት ብዙም አደገች የሚባልበት ደረጃ ላይ ያለመሆኗን ነበር።

አሁንም በፍርስራሾቹ ውስጥ እየተጓዝን ነው። እናም በአካባቢው ያገኘናቸው ነዋሪዎች እንደጠቆሙን ያለው ጎሚስታ አንድ ብቻ ነው። ወደዛው ሄድን በቦታው ስንደርስ የተነገረን ባለሙያው ወደ ሰርግ በመሄዱ የሚሰራልን አለመኖሩን ነው። ከመካከላችን አንደኛው በጣም ተግባቢና ቋንቋውን እዚህም እዛም እያለ የሚሞክረው ጋዜጠኛ የጎሚስታውን ባለቤት ስልክ አፈላልጎ ሊያመጣ በአካባቢው ከነበሩ ወጣቶች ሳይክል ላይ ተፈናጠጠ። እርሱ በሳይክል እኛም በእግር በዛላንበሳ አስፋልት መጓዙን ተያያዝነው። ባልደረባችን ስልክ ቁጥሩን ተቀብሎ ይመታ ጀመር። ከወዲያኛው ያለው ጥሪ ተሰማ። እና ያጋጠመንን ችግር ከመናገር አስቀድሞ ይህ ተወዳጅ ጋዜጠኛ ራሱን ማስተዋወቅ ቀጠለ ወዲያው በሌላኛው ጫፍ የነበረው ግንኙነት እንደተቋረጠ « ጢን ጢን » በሚለው ድምፅ አወቅን። በእርሱም እያሾፍን ተስፋ ባለመቁረጥ መልሰን ደወልን ስልኩ በድጋሚ ጠራልን ለማነጋገር ሄሎ ስንል ባለሙያው መኪናችን የቆመበት ቦታ እንደደረሰ ነገረን። ከወጣቱ በድርጊት የተረዳነው ለእኛ ሲል ሰርጉን የደስታውን ጊዜ አቋርጦ መምጣቱ ምን ያክል እንግዳ አክባሪ እንደሆነ ነው።

የመኪናችንን መሰራት ተስፋ በባለሙያው ላይ ጥለን ኢትዮጵያ የተባለ ሆቴል ደረስን። የሆቴሉ ባለቤት አባ ጠዓመ ስንገባ ጀምሮ በደስታ ነበር የተቀበሉን። የቆየ ታሪክም ይነግሩን ጀመር። ቦታውን ያገኙበት አጋጣሚ ሲያስታውሱም ልዑል ራስ መንገሻ ስዩምን ያገኙበትን ዕለት በመናገር ይጀምራሉ። ልዑል ራስ መንገሻን በአንድ ወቅት ያገኟቸውና ቦታ እንደሚፈልጉ ይገልፁላቸዋል። እናም ልዑሉ የት አካባቢ እንደሚፈልጉ ሲጠይቋቸው ምርጫቸው ዛላንበሳ እንደሆነ ይናገራሉ። ብዙዎች ስለቸርነታቸውና መልካም ሰውነታቸው የሚናገሩላቸው ልዑልም አሁን ኢትዮጵያ ሆቴል የተሰራበትን ቦታ ሰጧቸው። ይህን ታሪክ ከነገሩን በኋላም ለልዑል ራስ መንገሻ በአንድ ወቅት ምግብ ያቀረቡበትን የወርቅ ቅብ እንቁላል ቅርፅ ያለውን ዓሣ ነባሪ ሰሀን አምጥተው አሳዩን። ካባባ ጠዓመ ጋር ጨዋታው ደርቷል መኪናችን ግን አሁንም ተሰርቶ አላለቀም።

የመኪናችን ተሰርቶ አለማለቅ ግራ ቢገባን ባልደረቦቻችን እንደተለመደው ሳይክል ላይ ተፈናጠው መኪናው ከቆመበት ስፍራ ሄዱ። እናም መኪናው ተስፋ እንደሌለው ቁርጣችንን አወቅን። ይህን ጊዜ ነበር ሌላኛው አጋጣ ሚያችንን ልዩ ያደረገው ክስተት የተፈጠረው።

መኪናችን ካልተሰራ ሌላ ትራንስፖርት ይዘን ለመሄድ ተስማምተን መኪና በመጠባበቅ ላይ ነበርን። አንድ ያልነገርኳችሁ ነገር በዓዲግራት ቆይታችን በምግብ ምርጫ ዝርዝር ውስጥ የማይጠፋ "ቅንጥብጣብ" የተባለ ምግብ ዓይነት ነበር። እናም ከመካከላችን አንዱ «እንደው አሁንስ ይህ ቅንጥብጣብ ከአዲስ አበባ አብሮን የመጣ እየመሰለኝ ነው።» እያለ በምግብ ዝርዝር አይነት ውስጥ የማይጠፋውን "ቅንጥብጣብ መሰልቸቱን ከመግለጹ ከመቅፅበት የሆኑ ወጣቶች ከአጠገባችን ቆሙ። እነርሱም ቤት ገብተን ጠበል ቀምሰን መሄድ እንዳለብን ነገሩን። ያለምንም ማቅማማት እሺታችንን ገልፀን ታክሲ ጥበቃችንን ትተን ወደ ወጣቶቹ ቤት አመራን።

ስማቸውን ሲያስተዋውቁን የአንደኛው ወጣት መጠሪያ ትንሽ ግርምታን ጫረብን ሳተላይት ይባላል። ሌሎቹ አንገሶምና ሙሴ እንደሚባሉ ነግረውን ወደ ጎጇቸው አስገቡን። ቤት እንደገባን በአንድ ማዕድ ዙሪያ ተሰብስበን እንድንቀመጥ ተደረገ። እናት አንዱ ባንዱ ላይ የተደራረበ ወይንም ተሰቅስቆ የቀረበ እንጀራ በትሪ እንዲሁም ዝግኒ ወጥ በአማርኛው አጠራር በዘይት፣ በሽንኩርትና በበርበሬ ያበደ ልክ ለዶሮ እንደሚዘጋጀው ዓይነት ቁሌትና ሌሎች ለጥህሎ አስፈላጊ የሆኑትን ይዘው ብቅ አሉ። ለምግቡም ማወራረጃ ይሆን ዘንድ ስዋ (ጠላው) በሚኒልክ ቀረበልን። ሁሉም ነገር ለበጎ ነው ይባላልና እኛም የመኪናችን መበላሸት ለበጎ እንደሆነ እያሰብን ማዕዳችንን በጋራ ተቋደስን። እንግዳ አክባሪው የነ አንገሶም ቤተሰብ በላይ በላይ ወተቱን በጥህሎው ዙሪያ እያፈሰሰ እስክንጠግብ በላን።

ከነአንገሶም ቤት ተሰነባብተን ለከርሞ እንዲያገናኘን አድራሻ ተለዋውጠን ከቤት ከወጣን በኋላም ከቤታቸው አለፍ ብሎ ስላለው ሜዳ ጠየቅናቸው። ሜዳው ጋር በሚገኘው አስፋልት መኪና ማለፍ እንደማይችል ነገር ግን እግረኛ፣ ባጃጅና ጋሪ ብቻ እንደሚያልፉ ነገሩን። ጥያቄ ስራችንም ልማዳችንም ነውና ለምን እንደሆነ ስንጠይቅ ኤርትራ ፈቃደኛ ባለመሆኗ እንደሆነ መለሱልን። ገና ከመጀመሪያው ምስላችንን ማስቀረት የልባችን መሻት ነውና ይህንን ሳናስበው ልናሳካ መሆኑ ደስታችንን ጨመረው።

«ዛላንበሳ ቐረብ ማይ» የተባለ ታፔላ አጠገብ ቆመን ፎቷችንን ተነሳን። ትርጓሜው ዛላንበሳ ለውሃ የቀረበ እንደማለት ነው። ወጣቶቹ እንደነገሩን ሜዳው «አንበሰተ ገለባ» ሲባል እዛው ላይ በአንድ መስመር ወደ ላይ በግምት ከሶስት እስከ አምስት ጫማ ከፍታዎች የተከመሩት ድንጋዮች የኤርትራ ምሽጎች ነበሩ። እሰከ ቅርብ ጊዜ እዚሁ ሜዳ ላይ የህዝቡ በድንበር መለያየት ሳያግዳቸው ለግጦሽ የኤርትራም የኢትዮጵያም ከብቶች ይሰማሩበት እንደነበርና አሁን ግን ኢትዮጵያ መከልከሏን ነገሩን። ኧረ እንደውም አንዳንዴ ኢትዮጵያ ውስጥ ሚስት አልያም ባል ያላቸው ኤርትራዊ የዕድሜ ባለፀጎችም እየጠፉ ይመጣሉ። እናም ቤተሰባቸውን አይተው በፖሊሶች እንዲመለሱ ይደረጋሉ። በዚህ አጋጣሚም ከመካከላቸው አንደኛው ወጣት እናቱ ከሜዳው ማዶ በሚታየው የኤርትራ ግዛት ውስጥ እንደም ትኖር ፊቱን ቅጭም አድርጎ ነገረን። ብቻ በዕለቱ ብዙ ነገር አወቅን ለመጨረሻ ጊዜ ከተሰነባበትን በኋላም ትራንስፖርት ይዘን ባሻጋሪ በኤርትሪያ የሚታዩ የብርሀን ወጋገኖችን አርቀን እየተመለከትን ማምሻውን ወደ ዓዲግራት አመራን።

 

ፍዮሪ ተወልደ

Published in መዝናኛ

 

ጤና ይስጥልኝ ውድ አንባቢያን፡፡ እንኳን ለ2010 .ም አደረሳችሁ፡፡ የ2010 .ም የዘመን መለወጫ በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ማለፉን አይተናል፡፡ በዓሉን በማድመቅ በኩል የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ፕሮግራሞች ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ በቴሌቪዥን የሚቀርቡ የሙዚቃ ድግሶች፣ መዝናኛዎች፣ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቶች በዓሉን ከማድመቅ የዘለለ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ በክብረ-በዓላት ላይ የሚቀርቡ ዝግጅቶች ከሌላው ጊዜ የበለጠ ተደማጭ ናቸው፡፡ በተለያየ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የቤተሰብ አባላት አንድ ላይ ተሰብስበው በደስታ ይከታተሉታል፡፡ ይህ ተግባር ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በከፍተኛ መጠን እየተዘወተረ የመጣም ይመስላል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን ቋንቋዎች የሚሰራጩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን እያማረጥን መመልከት መቻላችን ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ አንዱ ጣቢያ ሲሰለቸን ሌላውን፤ የአንዱ ጣቢያ ፕሮግራም አልመጥን ሲል የምንፈልገውን ጣቢያ የመመልከት ዕድል ማግኘታችን «እሰየውየሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡ ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ባሳለፍነው የ2010 .ም የዘመን መለወጫ በዓል አብዛኞቹ የቴሌቪዥን ጣቢያዎቻችን ላይ አንድ ተመሳሳይ ተግባር ታይቷል፡፡ እርሱም እጅግ የተጋነነ ማስታወቂያ ነበር፡፡

እኔ እንደገባኝ ማስታወቂያ ምርትና አገልግሎትን በተመለከተ ለተጠቃሚዎች መረጃ በመስጠት የደንበኛን ቁጥር ማሳደግ ብሎም ገቢን መጨመር ነው፡፡ ትርጉሙ ከዚህ የተለየ ቢሆን እንኳን እኔ በዚህ መልኩ ስለተረዳሁት ለጊዜው እናንተም በዚህ መልኩ ተረዱልኝ፡፡ ምንም ይሁን ምን አንድ ማስታወቂያ ሲሰራ ምንን ታሳቢ አድርጎ ነው? ማስታወቂያውን በአየር ላይ የሚያውለው ተቋምስ ከሚያገኘው ዳጎስ ያለ ገንዘብ ያለፈ ሌላ ጉዳይ አይኖረውም ? የቴሊቪዥንና የራዲዮ ጣቢያዎች (የመንግስትም ይሁኑ ለንግድ ተቋቋሙት) የቀረበላቸውን ማስታወቂያ ሁሉ ተቀብለው ያሰራጫሉ እንዴ? ይህን ልል የቻልኩት ያለምክንት አይምሰላችሁ፡፡ የዘመን መለወጫ በዓል ዕለት በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሲተላለፍ የነበረውን ተደጋጋሚ የቢራ ማስታወቂያ መነሻ አድርጌ ነው፡፡

በርቬ የተባለ ተመራማሪ እና ጓደኞቹ በ2015 «ማስታወቂያ ከ13እስከ19 ዓመት በሚሆኑ ልጆች ላይ ያለው ተፅዕኖ» በሚል ርዕስ ጥናት አካሂደው ነበር፡፡ በዚህ ጥናት ህፃናት ልምድና ዕውቀት ስለሚያንሳቸው፤ እንዲሁም የማስታወቂያን ግነት ከተጨባጩ ዕውነት መለየት ስለማይችሉ የጥቃቱ ሰለባ ይሆናሉ። የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ጋልዳሳጅና እና ዊጄሱንዳራ የተባሉ አጥኚዎችም «በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች በህጻናት ባህርይ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያመጣሉ» ይላሉ፡፡ የጥናት ውጤታቸው ሕፃናት ተጨቃጫቂ እንዲሆኑ፤ የቤተሰብ አቅምን ያላገናዘበ ኑሮ እንዲመኙ፤ የጥራት ደረጃቸው የወረደ ምግብ ገዝተው እንዲመገቡና ለጤና ቀውስ እንዲጋለጡ ምክንያት ይሆናሉ ይላል፡፡

አሁን አሁንማ በቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጣቢያዎቻችን የሚተላለፈው የቢራ ማስታወቂያ የወተት ማስታወቂያ እየመሰለ መጥቷል ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ የስፖርታዊ ውድድሮች፣ ድራማዎች፣ ህዝባዊና መንግስታዊ በዓላት ስፖንሰሮች ቢራ ፋብሪካዎች ከሆኑ ሰንበትበት ብለዋል፡፡ በእርግጥ ሚዲያን ተደራሽ በማድረግ በኩል ለሚያደርጉት አስተዋፅዖ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ማስታወቂያዎች የሚቀርቡት ለማነው? አንዳንዶቹ ታዋቂ አርቲስቶችን ወይም ሞዴሊስቶችን ቢራቸውን አስጨብጠው በአስደማሚ አቀራረብ የሚፈልጉትን መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ፤ «18 ዓመት በታች ላሉት የማይሸጥ» የምትል የሰለለች ዓረፍተ ነገር ያቀርባሉ፡፡

በሌዚስተር ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ዲፓርትመንት በ2008 ያካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው የአልኮል ማስታወቂያዎች ልጆች በለጋ ዕድሜያቸው መጠጥ እንዲጀምሩ ምክንያት ከሚሆኑ ነገሮች ዋነኛው ነው፡፡ አጥኚዎቹ እንደሚሉት ልጆች ለአልኮል ማስታወቂያዎች መጋለጣቸው ቢያንስ ቢያንስ ያለዕድሜያቸው ስለመጠጥ እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ሐሳብ ደግሞ ወደ ተግባር ይቀየርና መጠጡን ይጀምራሉ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ቀን የገጠመኝን እንድ ምሳሌ ላንሳ፡፡ አንዲት ዕድሜዋ ከ6 ዓመት የማይበልጥ ልጅ በዘፈን መልክ «ሳብ ግጥም ዋንጫዬን አልለቅም» እያለች ባጠገባችን አለፈች:: «ሰማህ የሀገራችን ማስታወቂያ ውጤት» አልኩት አብሮኝ የነበረውን ባልደረባዬን፡፡ ሁለታችንም የማስታወቂያ ባለሙያዎች ባንሆንም የገባንን ያህል ጥቂት አወራን፡፡ «ሲጀመር ይህ አባባል ፀያፍ ነው፡፡ በጥልቀት ሲታይ ወሲብ ቀስቃሽ አንድምታ አለው» አለኝ ጓደኛዬ፡፡ «በኮምፒዩተር ታግዘው ለሚያስጨፍሯቸው ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋቾች የሚገባቸውን ክፍያ ፈፅመው ነው ወይስ መቸም ፈረንጅ አማርኛ አይሰማም ብለው ነው አልኩት፡፡ የዚህን ጥያቄ መልስ ጓደኛዬም አያውቀውም፡፡ «እኔ መልዕከቱም ግራ ያጋባኛል፡፡ ቢራ ብትጠጡ እንደእነዚህ ሰዎች ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋች ትሆናላችሁ ለማለት ነው? ወይስ እነዚህ ተጫዋቾች ጎበዝ ተጫዋጮች ሊሆኑ የቻሉት ቢራ ስለ ጠጡ ነው ለማት ይሆንአለኝ ፡፡ እኔ መልሱን አላወቅሁትምና እስቲ እናንተ ሞክሩት፡፡

አስተዋዋቂዎቹ የሚጠቀሙባቸው ክስተቶች (evenets) እና ግለሰቦች የማስታወቂዎቹን ተፅዕኖ ያጎላዋል፡፡ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ድራማዎች፣ ትዕይንቶች፣ የክበረ-በዓላት ዝግጅቶች በብዛት ስፖንሰር የሚደረጉት በቢራ ፋብሪካዎች ነው፡፡ በጣፈጠ አገላለፅና በሽልማት መባበያነት የቢራ አይነቶች የሚተዋወቁት በእነዚህ ፕሮግራሞች መጀመሪያ፤ በየመሃሉና በስተመጨረሻ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የእነዚህ ፕሮግርሞች ታዳሚዎች ደግሞ በብዛት እነማ ናቸው ? አዛውንት፣ ጎልማሳ ወይስ ወጣቶችና ህፃናት? ከዚህ በመነሳት እነዚህ ማስታወቂያዎች የሚቀርቡት ለማነው? የሚለውን መመለስ ካባድ የሚሆን አይመስለኝም፡፡

ሌለው ማስታወቂያውን የሚሰሩት ሰዎች ማንነትና ምንነትም ማስታወቂዎቹን በህፃናትና በወጣቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲያሳርፉ ያደርጋል፡፡ ታዋቂ አርቲስቶች፤ ቁመናቸው ያመረ ፤ ሰውነታቸው የወዛና ቁንጅናቸው የሚያማልል ወጣቶች ናቸው፡፡ ይህ ማስታወቂያ ተቀባይነት እንዲያገኝ እንደሚያደርገው ግልፅ ነው፡፡ የእነዚህ ሰዎች አድናቂዎች በብዛት የትኛው የማህበረሰብ ክፍል ይሆን? ህፃናትና ወጣቶች ወይስ ጎልማሶችና አዛውንቶች? በእርግጥ እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎችን ለመመለስ የዳሰሳ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ቢሆንም ግን የሰው ልጆች በየዕድገት ደረጃቸው የሚያሳዩትን የፍላጎት ዓይነት መሰረት በማድረግ መገመት ይቻላል፡፡ እንደነዚህ ሰዎች ታዋቂ ወይም ቆንጆ ለመሆን ዋናው ዘዴ ቢራ መጠጣት ነው ብሎ ሊያስብ የሚችለውስ በየትኛው የዕድሜ ክልል የሚገኝ ነው?

እንደሚታወቀው ዓውደ-ዓመት የቤተሰብ አባላት በዕድሜ ሳይገደቡ ተሰባስበው በጋራ የሚታደሙት ነው፡፡ እስቲ የትኛው ቤተሰብ ነው ከህፃናት ተለይቶ የክብረ-በዓል ማድመቂያ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን የሚመለከተው? የቢራ ማስታወቂያዎቹ የሚበዙት በእነዚህ ፕሮግራሞች ላይ መሆኑ ደግሞ የበለጠ በህፃናት ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ያደርጋቸዋል፡፡

ሌላው የሚገርመው ነገር የግልና የመንግስት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እኩል በዚህ ተግባር መጠመዳቸው ነው፡፡ እንዲያውም ፉክክር የገጠሙም ይመስላል፡፡ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ገቢ የሚሰበስቡትና ወጪያቸውን የሚሸፍኑት በማስታወቂዎችና ከአየር ሰዓት ሽያጭ ይመስለኛል (የሚዲያ ባለሙያ አለመሆኔን አስቀድሜ ስለገለፅኩ ከተሳሳትኩም ለመታረም ዝግጁ ነኝ)፡፡ የመንግስት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ግን ቢያንስ ቢያንስ አጀማመራቸው በህዝብ ገንዘብ ነው፡፡ እንደ ድርጅት ለመቀጠልና ተደራሽነታቸውን ለማስፋት ገቢ ቢያስፈልጋቸውም የተቋቋሙበት ዋናው ዓላማ ግን ገቢን ለማሰባሰብ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ለንግድ ከተቋቋሙቱ የበለጠ በትውልድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያመጡ ከሚችሉ ማስታወቂያዎች የመታቀብ ኃላፊነት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡

ከቢራ ማስታወቂያ የሚገኘው ገቢ ቢቀርባቸው እንኳን ስራቸውን የሚያቆሙ አይመሰለኝም፡፡ በግብር ከፋዩ ገንዘብ ለግብር ካፋዩ ጥቅም ሲባል የተቋቋሙ ናቸውና፡፡ ምንም እንኳን አሁን አሁን በራሳቸው ገቢ መተዳደር አለባቸው የሚል አሰራር ቢጀመርም፡፡ ቢሆንም ግን ገቢ የሚሰበሰበው በትውልድ ላይ አሉታዊ ድርጊት እየፈፀሙ መሆን የለበትም፡፡

ቢራ ፋብሪካዎቹ ምርታቸውን የማስተዋወቅ መብት የተጠበቀ ቢሆንም በተገቢው ቦታ ለተገቢው ታዳሚ መሆን አለበት ባይ ነኝ፡፡ ህብረተሰቡም ዝምታውን ሰብሮ መንግስት ልጆቹን ከአሉታዊ የሚዲያ ተፅዕኖ እንዲታደግ መጠየቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡

አንዳንድ ሀገሮች አልኮል በሀገራቸው እንዳይሸጥ የሚያግድ ህግ አላቸው፡፡ ቢሆንም ግን የድብቅ መሸታ ቤቶች በገፍ መኖራቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች ብዙ ናቸው፡፡ አልኮል በገሃድ በሚቸረቸርባቸው ያደጉት ሀገሮች እንኳን ዕድሜያቸው ላልደረሰ ልጆች እንዳይሸጥ የሚከለክል ህግ አላቸው፡፡ በእኛም ሀገር ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ልጆች አይሸጥም የሚል ነገር አለ፡፡ አፈፃፀሙስ ምን ይመስላል? የሚለው ግን «ውስጡን ለቄስ» ነው::ለነገሩስ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህፃናት በሚመለከቱት የቴሌቪዥን ድግስ ላይ «ቢራ ጠጡ እያሉ በማባበል ወዲያውኑ «ዕድሜያችሁ ከ18 ዓመት በታች የሆናችሁ ግን አትጠጡ» ማለት አግባብ ነው? በዘር ውርስ፤ በተፈጥሮ፤ በኑሮ ድሎት፤ በተስተካከለ አመጋገብ ወይም በሌላ ምክንያት የወዛና ያማረ ሰውነትን ቢራ በመጠጣት የተገኘ እያስመሰሉ በማቅረብ «ዕድሜያችሁ ከ18 ዓመት በታች የሆናችሁ አትጠጡ» ማለትስ «ከማለት» የዘለለ ትርጉም ይኖረዋል?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ የቢራ ማስታወቂያዎች በሽልማት ሎቶሪ ማባበያነት ታጅበው መቅረባቸው የጉዳዩን አስከፊ ደረጃ መድረስ ያመለክታል፡፡ «ቢራ ብትጠጡ አፓርታማ፤ መኪና፤ የቤት ዕቃ፤ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ትሸለማላችሁ» የሚል መደለያ በዝነኛ አርቲስቶችና በርቱዕ አንደበቶች እየቀረበ ነው፡፡ በአጋጣሚ ቢራ ጠጥተው ዕድሉ የገጠማቸውን በቴሌቪዥን መስኮቶች ብቅ አድርገው የምስክርነት ቃላቸውን ይቀበሏቸዋል፡፡ እንደ እኔ እንደ እኔ «የመንግስት ያለህ! የልጆቻችን ጉዳይ ከሁሉ በላይ ያሳስበናል» ማለት የሚገባን ደረጃ ላይ የደረስን ይመስለኛል፡፡ በመዝናኛ ቦታዎች፤ በሆቴሎችና በቤታችን ውስጥ እንኳን ለስላሳ መጠጦችን እንዳንጠጣ ልጆች ጫና እያሳደሩብን አይደለም እንዴ? «መኪና እንድትሸለም ቢራ ካልጠጣህ/ካልጠጣሽ» እያሉ የሚያዋክቡ ልጆች በየቤታችን ተፈጥረዋል፡፡ «መቸ 18 ዓመት ሞልቶኝ ቢራ ጠጥቼ የሚሉትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡

አንቱ የተባሉና በጡረታ ዕድሜ የሚገኙት ሳይቀሩ ቢራ በማስተዋወቅ ስራ ላይ ተሰማርተው እያየናቸው ነው፡፡ ለራሳቸው ቢራ እንደማይጠጡ የምናውቃቸው ለግላጋ ወጣት ተዋንያንስ ምን እያደረጉ ነው? እባካችሁ! ገንዘብ አላቂ ነው፡፡ ገንዘብ ይገኛል፤ ገንዘብ ይጠፋል፡፡ የትውልድ ቅብብሎሽ ግን ይቀጥላል፡፡ ለጨቅላዎቹ አስቡ፡፡ የእናንተ ገንዘብ ማግኘት ያስደስተናል፡፡ የሀገራችን ፈር-ቀዳጆቹ የጥበብ ሰዎች በድህነት ኖረው በድህነት እንደሞቱት እንድትሆኑ አንፈልግም፡፡ ሚሊየነር ለመሆን ብላችሁ ግን (የሆናችሁም ጭምር) የነገውን ሀገር ተረካቢ የሚጉዳ ተግባር አትፈፅሙ፡፡

አልበርት ባንዱራ የተባለው ታዋቂ የስነ-ልቦና ምሁር ሰዎች የሚመሩት መሰሎቻቸውን በማየትና በማስመሰል ነው ይላል፡፡ እንደ ባንዱራ አገላለፅ በተለይም ህፃናት የበላዮቻቸውን፤ ትልቅ ቦታ የሚሰጧቸውን ሰዎች በማየት፤ እነርሱ የሚያደርጉትን በማድረግ ይማራሉ፡፡ በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ መዋዕለ-ህፃናት ውስጥ ዕድሜያቸው ከ3እስከ6 ዓመት በሆናቸው 36 ወንድና 36 ሴት ህፃናት ላይ ሙከራ አድርጎ ነበር፡፡ ህፃናቱን በ3 ቡድን ከፈላቸውና ሰው መሰል አሻንጉሊትን (Bobo doll) የሚደበድብ ሰውን የሚያሳይ ፊልም ለ10 ደቂቃ እንዲመለከቱ አደረጋቸው፡፡ ቡድን አንድ ውስጥ የተመደቡ 24 ህፃናት አንድ ጎልማሳ ሰው አሻንጉሊቱን ሲደበድብና ይህን በማድረጉ ሲሸለምና ሲበረታታ የሚያሳይ ፊልም ተመለከቱ፡፡

በቡድን ሁለት ውስጥ የተመደቡት 24 ህፃናትም የተመለከቱት እንደ መጀመሪያዎቹ የድብድብ ፊልም ሲሆን ደብዳቢው ከድርጊቱ በኋላ ሲቀጣና ሲቆጡት የሚያሳይ ፊልም ነበር፡፡ በሶስተኛው ቡድን የተመደቡት ህፃናትም ተመሳሳይ ነገር ግን ደብዳቢው ሽልማትም ሆነ ቅጣት አለማግኘቱን የሚያሳይ ፊልም ተመለከቱ፡፡ በስተመጨረሻ የሶስቱም ቡድን ልጆችና ፊልሙን ያልተመለከቱ ሌሎች ልጆች በአሻንጉሊቱ እንዲጫወቱ አደረገ፡፡ ለራሱ ድብቅ ቦታ ሆኖ ጨዋታቸውን ይከታተል ነበር፡፡ በምልከታውም ወቅት ፊልሙን የተመለከቱ ልጆች ፊልሙን ካልተመለከቱ ልጆች የበለጠ በአሻንጉሊቱ ላይ የድብድብና የቁጡነት ባህርይ በጨዋታቸው ውስጥ ማሳየታቸውን መለየት ችሏል፡፡ በተጨማሪም ተደባዳቢው ሲሸለም የተመለከቱት ህፃናት ከሌሎቹ የበለጠ በአሻንጉሊቱ ላይ የድብድብ ሙከራ ሲያደርጉ እንደ ነበር ተረድቷል፡፡

ከዚህም በመነሳት ባንዱራ የሚከተሉትን ድምዳሜዎች ሰጥቷል፡፡ አንድም ህፃናት አዋቂዎች ከሚነግሯቸው ይልቅ አዋቂዎች የሚያደርጉትን በማየት ይማራሉ፡፡ ሁለትም ሽልማት ሌሎችን በማየት መማርን (ጥሩም ይሁን መጥፎ ) ያፋጥናል፡፡ ከዚህ ንድፈ-ሀሳብ አንፃር በሽልማት ታጅበው የሚቀርቡት የቢራ ማስታወቂያዎች ዕድሜያቸው ያልደረሰ ልጆች ቢራን እንዲጠጡ ቢያንስ ቢያንስ የጠጪነት ፍላጎት እንዲያድርባቸው የማድረግ ችሎታው በእጅጉ የላቀ ነው፡፡

ህፃናት የነገ ሀገር ተረካቢዎች ናቸው፡፡ እኛ ዛሬ የምናቀርብላቸው ትምህርት (በመደበኛም ይሁን በኢ-መደበኛ መልኩ) ነገ የሚሆኑትንና የሚያደርጉትን ይወስናል። በመንግስት ሚዲያ የሚተላለፉ ማናቸውም ፕሮግራሞች የመንግስትን አዎንታ ስላገኙ በተወሰነ መልኩ የመንግስትን ቢያንስ ድርጅቱን አቋም ያሳያሉ፡፡ በህዝብ ገንዘብ ለህዝብ አገልግሎት የተቋቋመ ሚዲያ ለንግድ ከተቋቋሙት እኩል ገንዘብ መሰብሰብ ላይ ከተጠመደ ህዝባዊነቱ ምኑ ላይ ነው?

በአጠቃላይ በሀገራችን የቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጣቢያዎች የሚሰራጩ የቢራ ማስታወቂያዎች ገደብ ቢበጅላቸው ጥሩ ነው ባይ ነኝ፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የመንግስት እና የክልል የቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ጣቢያዎች ዋና ዓላማቸውን ባይስቱ መልካም ነው፡፡ ገቢ ማስገባቱ አይጠላም፡፡ ነገር ግን በትውልድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያመጡ መሆን የለበትም፡፡ ስለ ዛሬው ገንዘብ ሲታሰብ ስለነገው ትውልድ መረሳት የለበትም፡፡ የሚገኘው ገንዘብ ምንም ብዙ ቢሆን እንኳን ትውልድን አይተካምና፡፡ ጆሮ ያለው ይስማ!

 

ካብታሙ አየለ (ረዳት ፕሮፌሰር)

 

 

Published in ማህበራዊ

ከግራ ወደቀኝ ፕሬዚዳንት ራምናት ኮቪንድ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፤

 

ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እያከናወነች ያለውን ስኬታማ ተግባራት የተለያዩ ዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙሃን በድረገጾቻቸው ለንባብ አብቅተዋል። በተለይም በኢኮኖሚው መስክ እየታየ ያለው ለውጥ፣ የውጪም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በማከናወን ላይ ያሉት ተግባራት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው ለመውጣት የሚያስችላቸውን አቅጣጫ እንደያዙ ዘገባዎቹ የዳሰሷዋቸው እውነታዎች ናቸው። ባለፈው ሳምንት መልካም ገጽታዎችን አጉልተው ካስነበቡት መካከል የኢትዮጵያ የስደተኞች አቀባበል ለዓለም አገራት ትምህርት ሰጪ መሆኑ፣ ኢትዮጵያና ህንድ በንግድና በመረጃ ልውውጥ ዘርፎች በጋራ ለመስራት መስማማታቸው፣ የቻይና ግዙፍ ኩባንያ የአፍሪካ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪን ተቀላቀለ የሚሉ እና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡ ፡

 

የኢትዮጵያ የስደተኞች አቀባበል ለዓለም አገራት ትምህርት ሰጪ ነው

በአሁኑ ጊዜ በርካታ አገሮች ዳር ድንበራቸውን በአጥር በመዝጋት ስደተኞችን ላለመቀበል በስደተኞች ላይ ጭካኔያቸውን በሚገልፁበት ወቅት ኢትዮጵያ ግን ጠላቷ ከሆነችው ጎሮቤት አገር ኤርትራ ሳይቀር የሚመጡ ስደተኞችን በደስታ ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ነች፡ ፡ ይህን የጠላት አገር ስደተኞችን ተቀብሎ ማስተናገድና በሀገሪቱ በርካታ ጥቅማ ጥቅሞች እንዲሰጣቸው ማድረግ ስትራተጂካዊ ምክንያት ሊኖረው ቢችልም በኢትዮ ኤርትራ ድንበር አካባቢ ካለው አስከፊ ሁኔታ ባሻገር 160ሺ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች በኢትዮጵያ ይኖራሉ፡፡ የሀገራቱ ተመሳሳይ ባህል መኖሩ ለስደተኞቹ ተድላ መሆኑንም ዘ ክርስትያን ሳይንስ ድረገጽ አስታውቋል፡ ፡

ስደተኞቹ በብዛት በመረብ ወንዝ አካባቢ ተሻግረው ኢትዮጵያ የሚገቡ ሲሆን ከኤርትራ ሲወጡ በደላሎች/የሰዎች አዟዟሪዎች/ በእግር አስፈሪውን ጉዞ በማድረግ ነው፡ ፡ በመንገድ ላይ አውሬዎች ያጋጥሟቸዋል፡ ፡ ይሁን እንጂ የኤርትራን ድንበር ተሻግረው ኢትዮጵያ አካባቢ ሲደርሱ በድንበሩ አካባቢ ያሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጥሩ አቀባበል አድርገው ወደ ሚፈልጉት ቦታ ደህንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ያደርሷቸዋል፡ ፡ የመከላከያ ሰራዊት አባሎች እንደ ወንድምና እህት ተንከባክበው እንደሚቀበሏቸው ስደተኞቹ ይናገራሉ፡ ፡

በኤርትራ ያለው ኢ-ሰብአዊ አያያዝና በመከላከያ ሃይሉ የሚያደርስባቸውን ስቃይና እንግልትን በመሸሽ በዘንድሮው ዓመት የካቲት ወር ብቻ ከሶስት ሺህ በላይ ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፡ ፡

የኢትዮጵያ የስደተኞችና ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ኃላፊ ኢስጢፋኖስ ገብረመድህን እንደተናገሩት፤ ልዩነቱ በአስተዳደሩ እንጂ በህዝቡ ሁለቱም ህዝቦች ተመሳሳይ ዓይነት ደምና የዘር ግንድ ያላቸው ናቸው፡ ፡ በተመሳሳይ በሁለቱም አገራት ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች የአንድ ቋንቋ /ትግርኛ/ ተናጋሪዎችና የተመሳሳይ እምነት /ኦርቶዶክስ/ ተከታዮች መሆናቸውን ነው፡ ፡

አንዳንድ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው፤ ችግሩ ያለው ከኤርትራው መንግስት እንጂ ከህዝቡ ጋር አለመሆኑን ይናገራሉ፡ ፡ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችም ስደተኞቹ ትምህርታቸን እንዲከታተሉ ይደረጋል፡ ፡ ምሁራንም ኢትዮጵያ ለስደተኞቹ በሯን ክፍት ማድረጓ ስትራተጂካዊ ምክንያት እንዳለው ይናገራሉ፡፡ በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ጥናት ያደረጉ በፕንሲይልቫንያ የአርካዲያ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ጀኒፈር ሪገን ስደተኞችን ማስተናገድ ለቀጣናዊ ግንኙነት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ኢትዮጵያ አጥብቃ ታምናለች ብለዋል፡ ፡ በቅርቡም በእንግሊዝ፣ አውሮፓ ሕብረትና ዓለም ባንክ በጋራ ለስደተኞች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርክ ለማስገንባት ይፋ መደረጉ ዘ ክርስትያን ሳይንስ ሞኒተር ድረገፅ ይዞት በወጣ ትንታኔ አስነብቧል፡ ፡

(The Christian Science Monitor 6

October 2017 Updated news)

ኢትዮጵያና ህንድ በንግድና በመረጃ ልውውጥ ዘርፎች በጋራ ለመስራት ተስማሙ

ኢትዮጵያና ህንድ በንግድ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና በሚዲያ ዘርፍ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ፡ ፡ የሕንዱ ፕሬዚዳንት ራምናት ኮቪንድ በብሔራዊ ቤተመንግሥት ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጋር በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡ ፡

የኢትዮጵያና ህንድ ግንኙነት በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን የህንዱ ፕሬዚዳንት ራምናት ኮቢንግ ገልጸዋል። የአገራቱ ግንኙነት ከኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት በተጨማሪ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር ሕንድ

ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል። በቀጣይም በጤና፤ ትምህርትና የሃይል ልማት ዘርፍ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር አብራ መስራት እንደምትፈልግ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ለኃይል ማመንጫ ግንባታ የሚውል 195 ሚሊየን ዶላር ብድር ለመስጠትም የሕንድ መንግሥት ቃል ገብቷል፡ ፡

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና ሕንድ ረጅም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰው የአሁኑ ስምምነት የሁለቱ አገራት ዜጎች በጋራ እንዲሰሩ ትልቅ መንገድ ይከፍታል ብለዋል። በቀጣይም የሁለቱን አገራት ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ በተለያዩ ዘርፎች ኢትዮጵያ ከሕንድ ጋር መስራት እንደምትፈልግ አስገንዝበዋል።

(News now Ethiopia 5 October 2017)

አንድ የቻይና ግዙፍ ኩባንያ የአፍሪካ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪን ተቀላቀለ

አንድ የቻይና ግዙፍ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ሀገራት ያለውን ቢዝነስ በተሳካ መልኩ ማስፋፋቱን ገለፀ፡ ፡ ‹‹ሊቦ›› በሚል የሚጠራው ይህ ኩባንያ ቻይና እ..አ በ2013 ይፋ ያደረገችው በ‹‹ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭ›› የትብብር ማዕቀፍ የፈጠረውን ምቹ እድልን ተከትሎ ነው በአፍሪካ ቢዝነሱን ያስፋፋው፡ ፡

‹‹ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭ›› ቻይና ከአፍሪካ፣ኢሲያና አውሮፓ ሀገራት ጋር በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣በመሰረተ ልማትና ኮንስትራክሽን ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር የፈጠረችው የትብብር ውጥን ነው፡ ፡ በዚህም መሰረት ..አ በ2006 የተቋቋመው ኩባንያው ይህንን ምቹ ዕድል በመጠቀም በተለይ በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ሀይል ዘርፍ ተሰማርቶ እንደነበር ተነግሯል፡ ፡

ባለፈው ዓመት ከበርካታ የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ጋር በመተባበርም 237 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ገንብቷል ተብሏል፡፡ 1 07 ሚሊዮን ዩዋን የተመዘገበ ካፒታል ያለው ኩብንያው፤ በስሩ 500 ሰራተኞችን ቀጥሮ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ተጠቅሷል፡ ፡ ኩባንያው ‹‹ቲቤት›› ከተባለ የቻይና ራስ ገዝ ክልል የወጣ ሲሆን ሌሎች ከ10 የሚልቁ ኩባንያዎችም በትብብር ማዕቀፉ የተፈጠረውን እድል በመጠቀም ቢዝነሳቸውን ወደ ሌሎች የአለም ሀገራት እንዳሸጋገሩም ተጠቁሟል፡ ፡

(Xinhua & EBC 5 October 2017)

 

ኢትዮጵያ የ75 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አገኘች

ራዲዮ ታማዛጁ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ዋቢ በማድረግ ባስነበበው ዘገባ፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ለምታከናውነው ተግባር ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች 75 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ማግኘቷን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ገለጸ።

አገሪቷ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ትግበራና የአየር ንብረት ከለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ለምታከናውናቸው ተግባራት ከፍተኛ በጀት እንደሚያስፈልጋት በሚኒስቴሩ የአየር ንብረት ለውጥ ትግበራ ማስተባበሪያ ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ደባሱ ባይለየኝ ተናግረዋል። ለእነዚህ ተግባራት ማከናወኛ በዓመት 7ነጥብ2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልጋት የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

ለትግበራው ውጤታማነት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ቢሆንም፤ ገንዘቡን በዘላቂነት ለማግኘት ለተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው። በመሆኑም ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ለአየር ንብረት ለውጥና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ትግበራ የሚያግዝ 65 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ መሰብሰብ ተችሏል።

በተመሳሳይ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም ለሚከናወኑ ተግባራት የሚውል 10 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተገኝቷል ነው ያሉት አቶ ደባሱ። ለተለያዩ ድርጅቶች የ50 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የድጋፍ ጥያቄ መቅረቡን ጠቁመው፤ በዚህ ወር መጨረሻ ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ለወሬ ምንጩ ተናግረዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም ለአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳ የምታደርገውን አስተዋጽኦ በማየት እገዛ ለማድረግ የሚመጡ አገራትን በማስተባበር የበጀት ምንጭ የማስፋት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

(Radio Tamazaju & ENA 6 October

2017)

 

በሞኒተሪንግ ክፍል

Published in ዓለም አቀፍ
Monday, 09 October 2017 19:44

ክርክር የወለደው ክርክር

   

አቶ ዘካርያስ ሄራኖ                           ወይዘሮ አንቺነሽ ተስፋዬ                   አቶ ተስፋይ ደገፍ

 

እንደ መነሻ

አቶ ዘካርያስ ሄራኖ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 40 ዓመት በላይ ኖረዋል፡፡ ለዘመናት የኖሩበት ቤት የእራሳቸው እንዳልሆነ በመግለፅ አግባብነት የጎደለው አሠራር እንዲሁም አስተዳደራዊ በደል እየደረሰባቸው ስለመሆኑ ለዝግጅት ክፍላችን አስረድተዋል፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 አስተዳደር በበኩሉ፤ ክሱ መሰረተ ቢስ ከመሆኑም ባሻገር ህጋዊ አሰራር እና ቅደም ተከተሉን ያልጠበቀ የመብት ጥያቄ በመሆኑ ለመቀበል መቸገሩን ይናገራል፡፡ በተጨማሪም ወረዳው በመልሶ ማልማት ውስጥ ያለ በመሆኑ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የተበራከቱበት እንደሆነ ያምናል፡፡ ይሁንና ሁሉም ጥያቄዎች ህጋዊ አሰራርን ተከትለው እስከመጡ ድረስ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች ይገልፃሉ፡፡

የአቶ ዘካሪያስ ጥያቄዎች

አቶ ዘካሪያስ 1981 .ም መንግስት ባወጣው ህግ መሰረት ክፍት ቦታ ካለ ቤት ሠርታችሁ መጠቀም ትችላላችሁ ስለተባለ አሁን ያሉበት ቦታ ላይ ቤት እንደገነቡ ይናገራሉ፡፡ ቦታውንም ከግለሰብ በስጦታ እንዳገኙ ነው የሚናገሩት፡፡ ሦስተኛ ወይንም አራተኛ ወራሾች ካልሆኑ በስተቀር ስጦታውን የሰጧቸው ግለሰብም ሆኑ በወቅቱ የነበሩት ምስክሮች አሁን በሕይወት የሉም፡፡ ይሁንና በፅሁፍ የተደገፈ መረጃ እንዳላቸው በመጠቆም አሁን እየኖሩበት ያለው ቤት ህጋዊ እና የራሳቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እርሳቸውን ጨምሮ ቤተሰባቸውን በከፍተኛ የኑሮ ጫና ውስጥ ስለሆኑ የንግድ ፈቃድ አውጥተው መስራት ይሻሉ።

አቶ ዘካሪያስ ሄራኖ በተደጋጋሚ 1138 የቤት ቁጥር የተመዘገበው የራሳቸው በመሆኑ ህጋዊ እውቅና እንዲሰጣቸው፣ ፈቃድ አውጥተው ለመስራትም የንግድ ፈቃድ ጥያቄ አቅርበዋል። እንዲሁም ቀደም ሲል በቤቱ ይገባኛል ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር ተከራክረው ማሸነፋቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ፍርድቤትም ቤቱ የእርሳቸው ስለመሆኑ የሚያስረዳ ፍርድ በመስጠቱ የንብረቱ ባለቤት እርሳቸው ስለመሆናቸው እንዲረጋገጥላቸው በርካታ ደብዳቤዎችን ለወረዳው ማመልከታቸውን ይናገራሉ፡፡ይሁን እንጂ ‹‹ቦታው የመንግስት ነው፡፡ ኪራይም አትከፍልም ስለዚህ ንግድ ፈቃድ አይሰጥህም›› ተባልኩ ይላሉ፡፡ ቀደም ሲልም በቤቱ ይገባኛል ጥያቄ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር ባደረጉት ክርክር በሁለት የፍርድቤት ውሳኔ ይዘው ቤቱም የራሳቸው ስለመሆኑ እንደተረጋገጠ የፍርድ ቤት መረጃ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ዳሩ ግን ወረዳው የፍርድቤት ውሳኔ ለማክበር ፈቃደኛ ባለመሆኑ ቅሬታቸውን ይገልፃሉ፡፡

አቶ ዘካሪያስ ሄራኖ መብታቸው እንዳይከበር፤ የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች ጫና እየፈጠሩባቸው እንደሆነ እና ህጋዊ መብታቸውን ለመጠየቅ በሚያደርጉት ጥረት ላይ እክል እየፈጠሩባቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በተለይ ደግሞ የሥራ አስኪያጁ እና የሥራ አስፈፃሚው ጫና የበረታ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡

«ሌላው ቀርቶ ጉዳዩ በህግ ተይዞ ለጥቅምት 06 ቀን 2010 .ም ብይን ለመስጠት በይደር የተያዘ ጉዳይ ነው፡፡ ይሁንና የወረዳው ሥራ አስኪያጅ ከደንብ ማስከበር ጋር በመሆን በሐምሌ ወር 2009 .ም መኖሪያ ቤቴ በር ላይ ወረቀት ለጥፈው ሄዱ» የሚሉት አቶ ዘካሪያስ በቀጠሮ ላይ እያለ እንዲሁም ጠበቃ አቁመው እየተከራከሩ ሳለ የመኖር ህልውናቸውን እያናጉት እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ «የመልካም አስተዳደር እጦትን በተመለከተ ጥያቄ ባነሳሁ ቁጥር ከባድ ጫና ውስጥ እየገባሁ ነው» ይላሉ፡፡ በተለይም በወረዳው ስላለው የመልካም አስተዳደር ግድፈት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሰላ ሂስ እየሰጡ በመሆናቸው ጥርስ ውስጥ እንዳስገቧቸው ያስረዳሉ፡፡

ከወራት በፊት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በወረዳው የነበረው የኪራ ሰብሳቢነት መንሰራፋት አስመልክቶ በአጀንዳ አምድ በወጣው የእርሳቸው ጽሁፍም ጫና እንደደረሰባቸው ያስታውሳሉ፡፡ አሁን በፍርድ ቤት በተያዘው ጉዳይ ከወረዳው ሥራ አስኪያጅ ዛቻ ተፈጽሞባቸው ለፖሊስ ቢያመለክቱም ጉዳዩ በቸልታ እንደታለፈና ስለመብታቸው በግልፅ ቢያስረዱም ሰሚ እንዳላገኙ በምሬት ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም እየኖሩበት ያለው ቤት የግለሰብ እንጂ ወረዳው እንደሚለው የመንግስት አይደለም ባይ ናቸው፡፡

የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ

በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 09 ሥራ አስኪያጁ አቶ ተስፋይ ደገፍ እንደሚሉት፤ ‹‹እንኳንስ አንድ ግለሰብ ጋር እሰጣ እገባ ውስጥ እጄን ላስገባ ቀርቶ መንግስት የሰጠንን ተልዕኮ ለመፈፀም እንኳን በቂ ጊዜ የለም፡፡ ስለዚህ ይህ ህጋዊ አሠራርን እና ደንብ ተከትሎ መፍትሄ የሚሰጠው እንጂ ግለሰባዊ ግጭትን የሚፈጥር ባለመሆኑ ክሱ አግባብ አይደለም›› ባይ ናቸው፡፡

ነገር ግን አቶ ዘካሪያስ 1984 .ም ወንድማቸው ቤት ለመጠለል መሸኛ እንዳመጡ ያስታውሳሉ፡፡ እናም የቤት ቁጥር 1138 የወንድማቸው ቤት ነው፡፡ አቶ ዘካሪያስ ደግሞ 1138/ለ ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ ይህ ቤታቸው ደግሞ ምግብ ማብሰያ የነበረ እና በሂደት የተሠራ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡ ቆርቆሮ ቤት ለመሥራት ለመንግስት አካላት ጥያቄ ማቅረባቸውንም ለአብነት በማንሳት የቤቱ ባለቤት አለመሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ይህ ቤት የአፈር ግብር እንኳን ያልተከፈለበት መሆኑን ነው የሚያስረዱት፡፡

«በአጠቃላይ አሁን የሚኖሩበት ቤት ከዋና ፋይላቸውም ሆነ ሌሎች መረጃዎች ሲጣራ የሚያሳየው ቤቱ የቀበሌ መሆኑን ነው፡፡በዚህም የግለሰብ ነው ማለት ያስቸግራል» ይላሉ፡፡ይሁንና በተለያዩ ወቅቶች ቅሬታ ማቅረባቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በዚህም መሰረት «ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ተመድቦ ጉዳዩን አጣርቶ ከውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡ በዚህም ቤቱ የእርሳቸው ባለመሆኑ ከመንግስት ተከራይ ሆነው እንዲኖሩ ቢነገራቸውም ፈቃደኛ አልሆኑም» ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 09 ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ወይዘሮ አንቺነሽ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ «በወረዳው ላይ በሥራ ኃላፊነት እስከተመደብኩ ድረስ ዜጎችን በእኩል ዓይን የማየት እና የማገልገልግ ሙያዊም ሆነ የሞራል ግዴታ ስላለብኝ አሁን የቀረበው ክስ ከስም ማጥፋት በዘለለ ትርጉም የለውም፡፡ ግለሰቡ አሁን ባለው ሂደትም በህግ አግባብ በመሄድ አልተከበረልኝም የሚሉትን መብታቸውን እንዲከበር ጥረት ማድረግ መብታቸው ነው» በማለት ነው ያለውን ሁኔታ የተናገሩት፡፡

«እንዲያውም አቶ ዘካሪያስ በወረዳው የሚፈፀሙ ህገወጥ ግንባታዎች እና ኢ-ህጋዊ ክንውኖችን የሚከታተሉ፣ መስመር እንዲይዝ መረጃ የሚሰጡ እንዲሁም ከህዝብ ክንፍ ጋር በሚደረጉ ውይይቶችም ጠቃሚ ሃሳብ የሚያመነጩ የወረዳው ነዋሪ ናቸው፡፡ በዚህም ጤናማ ግንኙነት እና ተግባቦት ያለ በመሆኑ ቅር የሚያሰኝ ነገር የለም» ይላሉ፡፡ ይሁንና እርሳቸው በተሰጣቸው ኃላፊነት ልክ በወረዳው ያሉ ጉዳዮች እንደሚከታተሉ እና ሁሉም በህግ አግባብ ፈር እንዲይዝ ጥረት በማድረግ ለአድሏዊ አሰራር በር መክፈት እንደሌለባቸው ይናገራሉ።

የቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ የውሳኔ ኀሳብ

አቶ ዘካሪያስ ሄራኖ ‹‹ወረዳው የሚያስተዳድረው ባልሆነው ይዞታዬ ወረዳው መብቴን ከልክሎኛል፣ የፍርድቤት ውሳኔ ተፈፃሚ አልሆነልኝም እና ለክፍለ ከተማው ወረዳው ቤቱን አስተዳድራለሁ ያለበትን ማስረጃ ጠይቄ ተከልክያለ›› ብለው ባቀረቡት አቤቱታ፤ አቶ ግርማ ኃይሉ፣ አቶ አሳዬ ዘላለም፣ አቶ ንማኒ ዱላ እና አቶ አብርሃም ግርማይ የተባሉ ግለሰቦች ሥም እና ፊርማ ባረፈበት እንዲሁም የውሳኔ ሃሳብ በተሰጠበት ሰነድ ላይ አቶ ዘካሪያስ ሄራኖ ጉዳይን እንዲህ ሲሉ ሪፖርት አድርገዋል፡፡

የቤት ቁጥሩ 1138 ‹‹አመልካች ምንም እንኳን በይዞታው ላይ ምንም መብት የሌለውን ቤተ ክህነት በፍርድቤት በመርታት የግሌ ይዞታ ነው በሚል ያቀረቡት የቤት እድሳት ፈቃድ ማስረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ሆኖ ሊያገለግል ስለማይችል፤ እንዲሁም ውሃ እና መብራት ያስገቡበት ማስረጃ ለማቅረብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ለመኖሪያ ቤቱ ኪራይ የተተመነበትንና ውሃ በመንግስት ስም ያስገቡበትን ደብዳቤ እንደ ማስረጃ በመጠቀም ቤቱ የመንግስት ነው በማለት የወረዳው ባለቤትነት በህግ አግባብ እንዲረጋገጥ በመደበኛ ፍርድቤት በአመልካች ላይ ክስ እንዲመሰረት የውሳኔ ሃሳብ አቅርበናል›› ይላል፡፡ ኮሚቴው በአቶ ዘካሪያስ ጉዳይ የውሳኔ ሃሳብ ለማቅረብም በ ‹‹25/01/94 .ም ስድስት ብር ኪራይ እንዲከፍሉ የተተመነበት፣ 28/01/94.ም ማስረጃ ባለማቅረባቸው ዕድሳት የተከለከሉበት እንዲሁም በ22/07/90 .ም ውሃ በመንግስት ሥም እንዲያስገቡ ደብዳቤ የተፃፈላቸው መሆኑ›› በአስረጅነት የዳሰሳቸውና ለውሳኔውም የተጠቀመባቸው መረጃዎች እንደሆነም ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም የቤቱ ሁኔታ ‹‹ያልተመዘገበ›› እንዲሁም ቤቱ ተመዝግቦ የሚገኝበት ሁኔታ ‹‹የራስ›› የሚል የተምታታ ሃሳቦችን ይዟል፡፡ ቅሬታው ያለውሳኔም ከጥቅም 07 ቀን 2007 ጀምሮ እስከ 21/09/2009 .ም በሰጡት ውሳኔ ላይ ተገልጿል፡፡

ከኋልዮሽ ታሪክ በጥቂቱ

በአሁኑ ወረዳ 09 በቀድሞ አጠራሩ ደግሞ ወረዳ 14 ቀበሌ07 አስተዳደር ሊቀመንበር ለአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት በማህተምና በቁጥር ተደግፎ ከፃፉት ደብዳቤ ውስጥ አንዱ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹በወረዳ 14 ቀበሌ 07 አስተዳደር ውስጥ በቤት ቁጥር 1ኛ አቶ ዘካሪያስ ሆራኖ የቤት ቁጥር 1138/ለ፣ 2ኛ ወይዘሮ መብራት ታደሰ የቤት ቁጥር 11363ኛ አቶ ፍቅሩ ደምረው የቤት ቁጥር 11404ኛ ወይዘሮ ዘነበች ወልደሃወሪያት የቤት ቁጥር 11335ኛ አቶ አንዳርጋቸው በየነ የቤት ቁጥር 1138 ነዋሪ የሆኑት ውሃ በመቅዳት ለችግር የተጋለጡ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህንን ችግር ለመቅረፍ እንዲቻል ውሃ እዲገባልን የትብብር ደብዳቤ ይፃፍልን ሲሉ ጠይቀውናል፡፡

ስለሆነም ከላይ ስማቸው እና የቤት ቁጥራቸው የተጠቀሱት የውሃ ችግር ያለባቸው በመሆኑ ይህንን ችግራቸውን ለመቅረፍ እንዲችሉ የቧንቧ መስመር ቤቱ የቀበሌ መሆኑ ታውቆ በቀበሌ ስም ውል ሞልተው ውሃው ቢገባላቸው በእኛ በኩል የምንደግፍ መሆናችንን እንገልፃለን›› ይላል፡፡

መስከረም 28 ቀን1994 .ም በዚሁ ቀበሌ ሊቀመንበር የተፃፈው ሌላኛው ደብዳቤ ደግሞ ‹‹በቀበሌያችን የቤት ቁጥር 1138/ለ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዘካሪያስ ሂራኖ የምኖርበትን ቤት ለማደስ እንድችል ፍቃድ ይሰጠኝ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ በዚሁ መሠረት የተጠቃሹ መኖሪያ ቤት ምንም ዓይነት ኪራይ የማይከፈልበትና ያልተተመነ በመሆኑ የዕድሳት ጥያቄ የሚፈቅደው የወረዳ 14 ሥራና ከተማ ልማት ጽህፈትቤት የይዞታ ማረጋገጫ በመፈለጉ ጥያቄያቸውን ለማስተናገድ ያልቻልን መሆናችንን እያሳወቅን ቤቱ ተተምኖ ሕጋዊ የሚሆንበት መንገድ ይመቻች ዘንድ ተገቢው መመሪያ እዲሰጥበት›› ሲል ለወረዳ 14 አስተዳደር ጽህፈትቤት አሳውቋል፡፡

ጉዳዩ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ ዘካሪያስ እንደሚሉት፤ እርሳቸው እና ወረዳው በይገባኛል የሚወዛገቡበት ቤት ጉዳይ በህግ አግባብ በመታየት ላይ እንደሆነ ለጥቅምት 06ቀን2010 .ም ብይን ለመስጠት ቀጠሮ መያዙን ያስረዳሉ፡፡

ሥራ አስፈፃሚዋ ወይዘሮ አንቺነሽ በበኩላቸው፤ በእነርሱ በኩል የፍርድ ቤት ቀጠሮም ሆነ ክስ እንዳልተጀመረ ይናገራሉ፡፡ ስለሆነም በፍርድ ሂደት ላይ ነው የተባለው መሰረተ ቢስ እና ከእውነታው የራቀ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡ ይልቁንም አቶ ዘካሪያስ ጋር ያለውን እሰጣ እገባ መፍትሄ እንዲሰጠው በህግ አግባብ ውሳኔ እንዲያገኝ ወደ ክስ ሂደት ለማምራት በሂደት ላይ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

መጨረሻው ምን ይሆን?

አሁን ባለው ሁኔታ አቶ ዘካሪያስ በቤቱ ውስጥ እየኖሩ ነው። ወረዳው ከቅሬታ አቅራቢው ጋር ከስምምነት ላይ ባለመድረሱ መረጃ አቀናብሮ፤ ፋይሉን አደራጅቶ ክስ ለማቅረብ ተዘጋጅቷል፡፡ መረጃዎችን አደራጅቶ እደጨረሰና ከህግ ክፍልም ጋር ምክክር እንዳደረገበት ይናገራል፡፡

አቶ ዘካሪያስ ሄራኖ በበኩላቸው፤ በቤቱ ውስጥ የተሻለ ኑሮ ለመኖር ባለቤታቸው በሰለጠኑበት ሙያ ስራ ለመስራት አስበዋል፡፡ በገቢም ራሳቸውን ለማሳደግ ህልማቸው ነው፡፡ ዳሩ ግን እርሳቸው ባሉበት ቤት ምንም ክፍያ ሳይፈጽሙ እየኖሩበት፤ ወረዳው በሃሳብ እንጥልጥል እደቀጠሉ ነው፡፡ «የንግድ ፈቃድ ይሰጠኝ፤ ሰርቼ ልለውጥ» የሚለው ጥያቄያቸው በተደጋጋሚ ለወረዳው ቢያቀርቡም ምላሽ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ የዚህን ክርክር መጨረሻ የዝግጅት ክፍሉም በይደር በጥያቄ ይዞታል፡፡ ለመሆኑ ለአመታት በክርክር የቆየው ቤት ለማን ይገባ ይሆን?

 

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

 

 

Published in ፖለቲካ

 በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አድአ ወረዳ ምርታማነቷ እና በጤፍ አቅርቦቷ ትታወቃለች። የቡልጋ፣ የጎጃም ጤፍ እንደሚባለው «የአድአ ጤፍ» የሚል ስም እስኪወጣለት ድረስ ምርቷ በመላ አገሪቷ ተፈላጊ ነው። በወረዳዋ የኤክስቴንሽን ቡድን መሪ የሆኑት አቶ አብነት አማኑኤል፤ በአካባቢው ያለው ሰብል ከተዘራ ሁለት ወራት እንዳለፉት ይናገራሉ። የወረዳው የመሬት ሽፋን 61 709 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል። የግብርና ግብአትን በመጠቀም በመስመር የተዘራው ደግሞ 93 በመቶ ይሆናል።

በዘንድሮ አመት የነበረው የዝናብ ስርጭት ለግብርናው አመቺ ነበር። ጤፍ ዝናብ ቢበዛበትም ተቋቁሞ ጥሩ ምርት የማፍራት ባህሪ ስላለው በወረዳው የጤፍ ምርት ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል። ዘንድሮ ከአጠቃላይ 833 ሺ ኩንታል በላይ የጤፍ ምርት በወረዳው እንደሚገኝ ይገመታል። ሽንብራ እና ጥራጥሬ ሰብሎች በበኩላቸው የዝናብ እጥረት ሊኖር ይችላል የሚል የተሳሳተ የአየር ንብረት ትንበያ በባለሙያዎች በመቅረቡ ምክንያት ቀደም ብለው እንዲዘሩ መደረጉን ያስታውሳሉ።

የተሳሳተው ትንበያም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ዝናብ በመገኘቱ የጥራጥሬ ሰብሎች ሊበላሹ ችለዋል። ችግሩን ለመከላከልም አርሶአደሮቹ የተዘራውን ማሳ ገልብጠው በማረስ በአነስተኛ እርጥበት ሊያድጉ የሚችሉ ሰብሎችን እያለሙ ይገኛል። በተለይ በጥቁር አፈር ላይ የውሃ ማጠንፈፊያ ሳያዘጋጁ ምርት ለመሰብሰብ በመነሳታቸው ምክንያት ሰብላቸው በውሃ ብዛት የተበላሸባቸው ጥቂት የወረዳው አርሶአደሮች ጓያ የተባለውን ሰብል በክረምቱ ወቅት ባገኙት እርጥበት አማካኝነት እንዲያለሙ እየተደረገ ይገኛል። በቀጣይም ከምግብ እጥረት እራሳቸውን ለመከላከል የጥቁር አፈር ማጠንፈፊያ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሙሉ በሙሉ ማምረት እንደሚገባቸው መግባባት ላይ መደረሱን ይናገራሉ።

በአድአ ወረዳ አምና ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ሰብል መገኘቱን የሚናገሩት አቶ አብነት፤ በዘንድሮ ምርት ዘመን አመርቂ ወጤት በአብዛኛው አርሶአደር ዘንድ በመታየቱ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ሰብል እንደሚመረት ባለሙያዎች መተንበያቸውን ይገልጻሉ። ከምርቱ ውስጥ አንድ ሶስተኛውን የሚይዘው የአድአ ጤፍ ነው። ቀጣይ ስራ ደግሞ በሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ምርቱን መሰብሰብ ይሆናል።

ነገር ግን በአካባቢው ኮንባይነር ተጠቅሞ የማጨድ አሰራር ባለመለመዱ በእጅ ስራው እንደሚከናወን ይናገራሉ። አሰራሩ ለምርት ብክነት የሚያጋልጥ በመሆኑም የኮንባይነር አቅርቦት በኪራይም ሆነ በሽያጭ ለአርሶአደሩ በአነስተኛ ዋጋ ቢቀርቡ አዋጭ መሆኑን ይናገራሉ። ከአጨዳ በኋላ ያለው የውቂያ ተግባር ግን በዘመናዊ መሳሪያዎች የሚከናወን በመሆኑ አርሶአደሩንም ሆነ እንስሳትን ከድካም እንደሚያላቅቅ ይጠበቃል። በወረዳው 21 ዘመናዊ የመውቂያ መሳሪያዎች ተዘጋጅተዋል። በቀጣይም ተጨማሪ መሳሪያዎች ለአርሶአደሩ እንደሚቀርቡ አስረድተዋል።

ከአድአ ወረዳ ወጣ ሲሉ በቆጂ ከተማን አልፈው አርሲ ዞን ዲገሉና ጢጆ ወረዳ ሲደርሱ የአርሶአደሮች ማሳ ለአይን በሚማርኩ ሰብሎች ተሞልቶ ያገኙታል። በአካባቢው ነዋሪ የሆኑት የአቶ ኤደአ ገመቹ ማሳ ግን አረም ወርሶት ቀጭጮ ይታያል። እርሳቸው እንደ ሌሎች የአካባቢው አርሶአደሮች የተትረፈረፈ ምርት የማግኘት እድላቸው አጠራጣሪ በመሆኑ የዕለት ውሏቸው በጭንቀት የተሞላ እንደሆነ ይናገራሉ። በአካባቢው ያለው የሙጃ እና የዋቅ አረሞች ሰብሎችን በብዛት እያጠፋ ይገኛል። በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ሶስት የተለያዩ የአረም ማጥፊያ መድሃኒቶችን ገዝተው ቢጠቀሙም ውጤታማ አልሆነላቸውም።

በተለይ «ፓላስ፤ ቶፒክና ናቱራ» የተባሉ አረም ማጥፊያዎችን ከግል አቅራቢዎች ላይ ገዝተው ተጠቅመዋል። «ነገር ግን ሙጃ አረሙ ከማጥፋት ይልቅ ሰብሉን ሸፍኖ እያደገ ይገኛል። አሁን ላይ አረሙን ለመንቀል ቢታሰብ እንኳን ስሩ ጥልቀት ያለው በመሆኑ የበቀለበትን አፈር ይዞ የሚነሳ በመሆኑ የሰብሉንም ስር አብሮ የመንቀል ችግር ሊያጋጥም ይችላል» ይላሉ። ስለዚህ አርሶአደሩ የወሰዱት እርምጃ ሰብሉ ለአጨዳ እስኪደርስ መጠበቅን ብቻ ነው። በአረም የተጎዳ እና አነስተኛ ምርት የሚሰጥ እንደሚሆን ስለገመቱ ለቀጣይ ምርት ጊዜ አስፈላጊው የመድሃኒት አቅርቦት እንዲመቻች ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛል።

በተለይ መንግስት ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ መድሃኒቶችን ቢያቀርብ ለአምራቹ አዋጭ እንደሆነ ይናገራሉ። ከየአካባቢው የሚገዛው መድሃኒት ግን ውጤት የማምጣት ሁኔታው እየቀነሰ ይገኛል። ጊዜው ያለፈበትና አረም የማያጠፋ መድሃኒት በገጠራማ አካባቢዎች የሚያቀርቡ ሰዎችንም በህግ መጠየቅ እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ።

በአርሲ ዞን ገብስ አምራች የሆኑት አርሶአደር ፊጣ አበበ ግን የአቶ ኤደኦ እጣ ፋንታ ስላልገጠማቸው ሰብላቸው ያማረ ፍሬ ይዞላቸዋል። በመስመር የተዘራው ገብስ አረሙ ሲደርስ ኬሚካል የማያጠፋው መሆኑን በመገንዘብ በየሁለት ቀኑ የሚበቅሉ አረሞችን የማጥፋት ዘመቻ ከቤተሰባቸው ጋር ማከናወን ችለዋል። በዘንድሮ አመት የሚገኘው ምርትም የተሻለ ጥራት እና ብዛት እንደሚኖረው ተስፋ አላቸው። የተለያዩ የግብርና ባለሙያዎች የሚያደርጉት ድጋፍም ለግብርና ስራቸው መሻሻል ወሳኝነቱ የጎላ መሆኑን ያምናሉ።

በአካባቢው በሚገኙ እያንዳንዱ ቀበሌዎች ውስጥ ቢያንስ ሶስት ባለሙያዎች እንደሚመደቡ ይናገራሉ። የመጀመሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ፣ የተፈጥሮ ሃብት ባለሙያ እና የእንስሳት ሃብት ባለሙያዎች ናቸው። የልማት ጣቢያ ሰራተኞች በተለይ የአመራረት ዘዴን በማስተማር ረገድ በመስመር እንዲዘራ በማድረጋቸው በሄክታር የአምስት ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት እንዲገኝ ማገዛቸውን ይናገራሉ። በቀጣይ ደግሞ ዘመናዊ የመስመር መዝሪያ ማሽኖችና የድህረ ምርት መሰብሰቢያ እና ማከማቻ መጋዘኖች እንዲስፋፉ ከተደረገ አገሪቷ ህዝቦቿን መመገብ የሚያስችል ምርት እያዘጋጀች መሆኑን ይገልፃሉ።«እያንዳንዱ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በምርት ላይ የሚያሳድረውን በጎ ተጽእኖ በመረዳት አርሶአደሩ ለቴክኖሎጂ ያለው አመለካከት ከፍተኛ ሆኗል። አቅርቦቱ እና ፍላጎቱ ሲነጻጸር ግን የአርሶአደሩ ጥያቄ እያየለ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። በመሆኑም ትኩረት የሚያስፈልገው የምርት ወቅት እና የድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብ ነው» በማለት ያስረዳሉ።

የአርሲ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አደም ቦሼ አርሲ ላይ በአመት ሁለት ጊዜ ማለትም ክረምትና መኸር ላይ ዝናብ የሚገኝ በመሆኑ ከመስኖ ልማት በተጨማሪ ሁለት ጊዜ የማምረት እድል መኖሩን ይገልፃሉ። የቅድመ ምርት ዳሰሳ መረጃ እንደሚያመለክተው በዘንድሮ የምርት ጊዜ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። የመኸር ወቅትን በተመለከተ በአጠቃላይ 596 ሺ ሄክታር የሚለማ በመሆኑ ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝ ተገምቷል። በማሳ ላይ የሚታየውም ውጤት እቅዱን ለማሳካት የሚያስችል ምርት እንዳለ ያመላክታል። ከባለፈው አመት በየተሻለ ምርት እንደሚገኝ መታመኑን ይገልፃሉ።

የአርሶአደሩ የግብአት አጠቃቀም ከቀድሞ የተሻሻለ መሆኑን በመጠቆም የማዳበሪያ አጠቃቀም ባለፈው አመት በተለያዩ የአቅርቦት ችግሮች ምክንያት ከሶስት መቶ ሺ በላይ እንዳልተሰራጨ ይናገራሉ። ዘንድሮ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር ተፈጥሮ አንዳንድ አርሶአደሮች ቀድመው ላዘጋጁት እርሻ ሳይደርስ ቀርቷል። ነገር ግን ዘግይቶም ቢሆን በደረሰው ማዳበሪያ ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በመጠን የ135 ሺ ኩንታል ጭማሪ አሳይቷል። በተጨማሪ የምርጥ ዘር ግብዓት እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ታሳቢ በማድረግ የተሻለ ምርት እንደሚገኝ ይገመታል።

አንዳንድ አርሶአደሮች ላይ የተከሰተውን የአረም ችግር በተመለከተ ዞኑም ለቁጥጥር አስቸጋሪ እንደሆነበት ይገልጻሉ። አንዳንድ የአረም ዝርያዎች በምንም አይነት ኬሚካል ሊጠፉ ባለመቻላቸው ለአካባቢው አመራር እና አምራች የእራስ ምታት ሆነው እንደቀጠሉ ይገኛል። አንዱ የሙጃ የሳር አረም ሲሆን ለአርሶአደሮቹ የሚቀርቡ የተለያዩ ኬሚካሎችን ተቋቁሞ ሰብል ላይ ጉዳት ያደርሳል። በመሆኑም አስቸጋሪ አረሞችን መከላከሉ ለተመራማሪዎች የቤት ስራ ሆኗል። የምርምር ማዕከላት በገጠራማ አካባቢዎች አየር ንብረቱን እና የተለያዩ ኬሚካሎችን ተቋቁመው ጉዳት የሚያደርሱ አረም እና በሽታዎችን በመከላከል ረገድ ሰፊ ስራ ይጠበቅባቸዋል። በአገር ደረጃ መፍትሄ የሚያስፈልገው የአረም ችግርን መፍትሄ ከተበጀለት የምርት መጠኑን ከፍ ማድረግ የሚያስችል አቅም መሆኑ አያጠያይቅም።

 

ጌትነት ተስፋማርያም

Published in ኢኮኖሚ

 

አንድ እውነት አለ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔና የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የከተማይቱን የውሃ ፍላጐት ለማርካትና ተደራሽነቱን ለማስፋት እጅግ በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል። ንፁህ የመጠጥ ውኃ ከማምረት አንስቶ እስከ ማከፋፈል ድረስ በውኃ ረገድ ጥሩ ቁመና ላይ መገኘቱን የሚያረጋግጡ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል። የከተማው መስተዳድር ከራሱ የገንዘብ ቋትና ከፌዴራል መንግሥትና በእርሱም አማካይነት የተገኘውን 10 /አስር/ ቢሊዮን ዶላር ለውሃ ሥራ ፕሮጀክቶች አውሏል። የዛሬ ዓመት ከነበረብን ውኃን በጄሪካን በሸክም ከማመላለስ ችግር በግማሽ ያህል በቀነሰ ሁኔታ ላይ እንገኛለን። ችግሩ በባሰባቸው አካባቢዎች ማዕከላዊ ስፍራዎች ላይ ትላልቅ ሮቶ በርሜሎችን በመትከል ውኃ በቦቴ እያመላለሰ በመሙላት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጓል። ሰርቷል! እየሰራም ነው! እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም።

ይሁን እንጂ መስተዳድሩና ባለሥልጣኑ የቱንም ያህል ቢንቀሳቀሱ የውኃ ችግራችን ዛሬም ድረስ አልተፈታም። በውኃ ረገድ ፍትሃዊ ተደራሽነት የለም። ዓመቱን ሙሉ ውኃ ለደቂቃ የማይቋረጥ ባቸው፤ በፈረቃ በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ውኃ የሚመጣባቸው፤ አካባቢዎች አሉ። ከወር እስከ ወር የማያገኙ ቦታዋችም አሉ። የአፍሪካ የውኃ ማማ እየተባለች የምትወደስ አገር ዛሬ ለህዝቦቿ የእግዜሩን ውኃ ለማዳረስ አቅም አጥሯታል።

የንፁህ ውሃ አመራረታችን ተደራሽነታችንና ፍትሃዊ ተጠቃሚነታችን እንዲረጋገጥ የውኃ አስተ ዳደራችን ቁመና ደግመን ደጋግመን መፈተሽ አለብን። የአገልግሎት አሰጣጣችንን ማሻሻል ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ግን አልተቻለም። ይህ በሆነበት ሁኔታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔና የውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን አንድ ዕቅድ ይዘው ብቅ ብለዋል። «የውኃን ነገር ለማሻሻል የውኃ ታሪፍ ጭማሪ ማድረግ» ይሰኛል። የሰሞኑ የህዝብ መነጋገሪያ አጀንዳም ይኸው የታሪፍ ጭማሪ ጉዳይ ነው። ለታሪፍ ጭማሪው እንደምክንያት የተጠቀሰው የአዲስ አበባ ታሪፍ ከሌሎች ከተሞችና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ በመሆኑና አሁን ያለው የታሪፍ ምጣኔ ዝቅተኛ በመሆኑ ባለሥልጣኑ ለሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች ሁነኛ የፋይናንስ ምንጭ ሊሆን ስላልቻለ መሆኑ ተነግሮናል።

ጠቅላይ ሚኒስትራችን ምስጋና ይግባቸውና ይህን የታሪፍ ጭማሪ ሃሳብ ውድቅ አድርገው ተግባራዊ እንዳይሆን አግደውታል። ዋጋ ከመጨመር በፊት የአገልግሎት አሰጣጡን የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ አለብን ብለዋል። ትክክለኛው ውሳኔም ይህ ነው። መፍትሄው ያለውን የሌሎችን ከተሞች ታሪፍ በማየት ላይ አይደለም። የምንኖረው እንደየቤታችን እንጂ እንደ ጐረቤታችን አይደለም። በመሠረቱ ታሪፍ መጨመር ወግ አይደለም። በአንድ ገጽ ወረቀት ላይ ጽፎ «አዋጅ ነው» ብሎ መለጠፍ ነው። «የውኃ ታሪፍ የጨመረ በመሆኑ በሜትር ኩብ ሁለት ብር የነበረው ከ------ ቀን ጀምሮ በሜትር ኩብ አምስት ብር መሆኑን እናስታውቃለን።» ማለት ብቻ ነው። የቀልድ ያህል ቀላል ነው። ችግሩ ግን በቀልድ አይፈታም።

ችግሩ በዋነኛነት የሚፈታው የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ብቻ ነው። አገልግሎቱ ሲሻሻል ማለት ውኃን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ማለት ብዙ ህዝብ ብዙ ሜትር ኩብ ውኃ እንዲያገኝና እንዲጠቀም ማድረግ ነው። ህዝቡ ውኃ አግኝቶ ሲጠቀም መንግሥት በሜትር ኩብ ሁለት ብር ስሌቱ ቤቱ ብቻ ለፕሮጀክቶቹ የሚውል ሁነኛ የገንዘብ ምንጭ ያገኛል። የታሪፍ ጭማሪ ማድረግም ላያስፈልገው ይችላል። ከውኃ የሚሰበሰበው ታሪፍ አጠቃላይ ገቢ ያነሰው የታሪፉ ምጣኔ (በሜትር ኩብ ሁለት ብር) አንሶ ሳይሆን ውኃው ለተጠቃሚው ህዝብ በተገቢ መጠን ባለመቅረቡ ነው። የአገልግሎት አሰጣጡ ባለመሻሻሉ ነው። በሳምንት አንድ ቀን ለዚያውም ለተወሰነ ሰዓት ያውም በብርድና በዝናብ ውስጥ መከራውን እየበላ ውኃ ሲጠብቅ ለሚያድረው ህዝብ የታሪፍ ጭማሪ ማድረግ ፌዝ ነው። ህዝቡ የሚለው «ውኃ አቅርብልኝና ልግዛህሲሆን መንግሥት ደግሞ «የምሸጥልህ ውኃ የለኝም ዝም በልና ክፈልነው። መግባባት አይቻልም። «አገልግሎት ስጠኝ ... ልክፈል» ያለዚያ ለምን ብሎ ይከፍላል። ለየትኛው ውለታው ነው ህዝቡ መቀነቱን እየፈታ ታሪፍ ጭማሪ የሚከፍለው? የማይሆን ነገር ነው። በንግድ መመሪያውም ላላገኘኸው አገልግሎት «ክፈል» የሚል ሕግ የለም። ውኃና ፍሳሽ ባዶ እጁን እየመጣ እኔን ገንዘብ አምጣ ሊለኝ አይችልም። በዚያችው የውኃ መስመሬን ለመቁረጥ ካለችው ጉልበት በስተቀር ህጋዊ መሠረት የለውም።

ሌላው ቀርቶ በሳምንት አንድ ቀን የሚለቃትን ውኃ በሳምንት ሁለት ሦስቴ ቢያደርጋት በሁለት ብር ታሪፍም ቢሆን ገቢው ከፍተኛ ይሆንለታል። አንድ ባለ20 ሊትር ቢጫ የዘይት ጄሪካን ውኃ አስር ብር ከመግዛት ገላግለንና ብትፈልግ ታሪፍ ጨምርብን።ውኃ በሌለበት አገር ታሪፍ መጨመር ግን «ፌር» አይደለም። አገልግሎትን አሻሻሎ ውኃውን ተደራሽ ቢያደርግልን ያለምንም ችግር ሂሳቡን ከቆጣሪያችን ላይ እያነበበ መሰብሰብ ይችላል። ምንም ጭቅጭቅ አያስነሳም እያንዳንዱ ህዝብ የሚከፍለው የተጠቀመበትን መጠን ያህል ነው። ማስረጃውም የቆጣሪ ንባቡ ነው።

«ታሪፍ አያስፈልግም» አንልም። ታሪፍ የመንግሥት ገቢ ለማሳደግና የበለጠና የተሻለ አገልግሎት ለማቅረብ አንዱ ዘዴ መሆኑን እናምናለን። ነገር ግን አማራጭ አለን። የውሃ አቅርቦት አገልግሎታችንን በማሻሻል ከቆጣሪ ንባባችን ላይ ብቻ ማግኘት እንችላለን። ታሪፉ ለጊዜው ይለፈን።የእኛ ሰው ደግሞ «ጭማሪ» የሚለውን ቃል በተመለከተ የራሱ ጠባይ አለው። ሲጨመርለት እንጂ ጨምር ሲሉት አይወድም። ከብዙ ዓመታት በፊት አንድ የማውቀው ገጠመኝ አለ። አንዱ ሰውዬ ላይ የውሃ ጭማሪ ሂሳብ 25 ሳንቲም መጣበት። «ታሪፍ ጨምሮ ነውአለ «አይደለም» ተባለ። የተጠቀምክበት የቆጣሪ ንባብ ነው አሉት። «እንዴት እኔ ይሄን ያህል ውኃ እጠቀማለሁ ዝሆን አላረባም... ግመል አላጠጣም... ምን ሲደረግ የስሙኒ ብልጫ መጣብኝ» ብሎ ሥራውን ፈትቶ ውኃ ክፍል ድረስ ሲመላለስ ከረመ። ሊቀንሱለት አልቻለም። ከዚያማ ተከራዩን ሁሉ አመሰው። ውኃ ጨምሯልና ሁላችሁም በቤቱ ኪራይ ላይ የውኃ አምስት አምስት ብር ጨምሩ አለዚያ ልቀቁ አለ። እሱ ላይ የተጨመረበት ሃያ አምስት ሳንቲም ብቻ ሲሆን በአራት ተከራዮች ላይ በአምስት ብር ሂሳብ ሃያ ብር ቆለለብን። አማራጭ አልነበረንም ከፈልን። በቤቱ ባለቤት ላይ የመጣች የስሙኒ ጭማሪ የተከራዮቹን አምስት ብር በነፍስ ወከፍ ይዛ ሄደች።

የጭማሪው ጫና ሁልጊዜም የሚያርፈው በተጠ ቃሚው ደሃ ህዝብ ትከሻ ላይ ነው። ታሪፍም ጨመረ፣ የቆጣሪ ንባቡም ጨመረ ዕዳው የተጠቃሚው ነው። ህዝቡ ደግሞ ይህንና ሌሎች በየሰበቡ የሚመ ጡበትን ጭማሪዎች የሚሸከምበት አቅም የለውም። ግብር ተጨመረ ሲባል ነጋዴው በህዝቡ ላይ ይጨምራል።«እኔ ምን ላድርግ መንግሥት ነው የጨመረው» እያለ ህዝብና መንግሥትን ያጋጫል። በዚህ ላይ ሌሎች መዋጮዎችም አሉበት። ምንም እንኳ የመዋጮዎቹ ዓላማ ለልማትና ለእድገት ቢሆንም በህዝቡ የእለት ተእለት ህይወት ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም።

አጠቃላይ የኑሮ ውድነትም አለ። ቤት ኪራይ አይቀመስም የትራን ስፖርት የልጆች ትምህርት ቤት የየቀን የቤት ወጪዎችና ፍጆታዎች ሁሉ አስቸጋሪዎች ናቸው። ውኃ ደግሞ ከሌሎች ፍጆታዎች ሁሉ አስፈላጊ የሆነ መሠረታዊ ፍጆታ ነው። ለህይወት ዋናው አስፈላጊ ነገር ውኃ ነው። አገልግሎቱን ማሻሻል የግድ ያስፈልጋል። በውኃ ጉዳይ ህዝቡ ተማሯል። ስለውኃ ታሪፍ ጭማሪ ካነጋገርኳቸው ሰዎች መሃል «ጭማሪው መፍትሄ አይደለም» ሲሉ «ምን ይሻላልሲባሉ የአዲስ አበባን አጠቃላይ የውኃ አገልግሎት ተደራሽነት ለማረጋገጥ ሥራው ለቻይና ኩባንያውች ቢሰጥ ይሻላል» የሚሉ አሉ።

እንዲህ አይነት ሰሜት ውስጥ በሚገኝ ተጠቃሚ ላይ ታሪፍ ጭማሪ አቅድ ላይ የወሰዱት የእገዳ እርምጃ እጅግ በጣም ተገቢ ነው። ውሳኔ ማለትም ይሄ ነው። የአመራሩ ጥንካሬ ብዙ እርምጃዎች መጓዙን የሚያሳይ ታላቅ እርምጃ ነው። በሙሉ ድምፅ ደግፈነዋል። በቀረበ ሰነድ ሁሉ መፈረምና ማፅደቅ ብቻ ሳይሆን ለህዝብ ጥቅም ሲባል ማገድ ከታላቅ አመራር የሚጠበቅ ነው።ፈጣሪ ይስጥልን! ጌታ ያክብርልን!

 

ግርማ ለማ

Published in አጀንዳ

 

ግብርና የአብዛኞቹ የሀገራችን ህዝቦች መተዳደሪያ እና የገቢ ምንጭ ነው። የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ፣ የአግሮ ኢንዱስትሪ ልማታችንን ለማፋጠንና ለወጪ ንግዳችን ማደግ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። በአጠቃላይ ለኢኮኖሚ እድገታችን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው ዘርፍ ነው፡፡

ትክክለኛ ፖሊሲ በመቅረፅ ግብርናና ገጠር ልማትን ማዕከል በማድረግ ለቴክኖሎጂ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራት ላይ ነው። የማስፋት ስትራቴጂ ተቀርፆ ማልማት በመጀመሩ በተለይ ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ የሆነ የምርታማነት እድገት እየተመዘገበ ይገኛል፡፡ በዘንድሮው የመኸር እርሻ በክላስተር ተደራጅተው፣ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያን የመሳሰሉ ሙሉ ፓኬጆችን ተጠቅመው ማሳቸውን በዘር የሸፈኑ አርሶ አደሮች በማሳቸው ላይ የሚገኘው የሰብል ይዞታ አመርቂ መሆኑን እየተናገሩ ነው። ይዞታው በውጤት እንዲደመደም ቀሪ የግብርና ስራዎች ላይ መረባረብ ይገባል።

በሰብል፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ ሀብት መስኮች አመርቂ የሚባል ሳይንሳዊ የምርምር ተግባራት እየተከናወኑ ነው። ለግብርና ልማቱ ግብዓት የሚሆኑ የተሻሻሉ ተፈጥሯዊና ሥነ ህይወታዊ ችግሮችን የሚቋቋሙ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና መረጃዎችን በማቅረብ ስኬታማ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ይህ በሌሎች መስኮች ከተሰሩት ተግባራት ጋር ተዳምሮ ግብርናችን እያስመዘገበ ለመጣው ፈጣንና ተከታታይ እድገት የጎላ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

የምርምር ተቋሞቻችን በተለያዩ ሰብሎች ላይ በመመራመር የምርታማነታቸውን ደረጃ በማሻሻል የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ሂደት ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ ለውጭ ገበያ በሚቀርቡት እንደ ቡና፣ ሰሊጥና ጥራጥሬ ሰብሎችም ወጤታማ ዝርያዎችን በማላመድ፤ የአመራረት ዘዴን በማሻሻል፤ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብና ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ብዛትና ጥራት በማሳደግ፤ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት መሻሻል ከፍተኛ እገዛ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

በተለይም ገበያ ተኮር የሆኑትን እንደ የዳቦና የፓስታ ስንዴ፣ የቢራ ገብስ፣ የጥጥ እና የቅባት ሰብሎች ለመሳሰሉ የአግሮ ኢንዱስትሪ መሠረታዊ የግብአት ምርቶች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል። የተሻሻሉ ዝርያዎችንና የአመራረት ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች የግብዓት መጠንን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ከውጭ የሚገባውን ግብዓት ደረጃ በደረጃ በመቀነስ የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለማዳን ለተቀመጠው አገራዊ ግብ የሚጠበቅባቸውን ውጤት እያስመዘገቡ ነው፡፡

የምርምር ተቋማቶቻችን ያቀረቧቸው ነገር ግን ገና አሟጠን ያልተጠቀምንባቸውና ያልደረስንባቸው የምርታማነት ደረጃዎች እንዳሉን አይካድም። በቀጣይ በማስፋት ስትራቴጂው ላይ በመመስረት የተሻሻሉ ዝርያዎችና በምርምር የተገኙ ግብአቶች ለሁሉም ተጠቃሚዎች እንዲደርሱና ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ አሁንም በርካታ የግብርናው ዘርፍ ችግሮች የተሟላ መፍትሄ ያላገኙ በመሆኑ ምርትና ምርታማነት በሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም። ዘርፉም በሚጠበቀው ደረጃ ሽግግር አላደረገም፡፡ በመሆኑም እንደ ሀገር የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ቢቻልም በቤተሰብ ደረጃ ገና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አልተቻለም። የግብርና ኢንዱስትሪውን ፍላጎት የሚያረካ በቂ የግብርና ምርት አልቀረበም። የግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ በመጠን፣ በዓይነትና በጥራትም ገና ብዙ እንደሚቀራቸው ይታመናል፡፡

ስለሆነም በቀጣይ የምርምር ተቋሞችን የመመራመር አቅማቸውን የበለጠ በማሳደግ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ረገድ ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከቴክኖሎጂ አቅርቦት አኳያ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሚያደርጉን የላቀ ምርታማነትና ጥራት ያላቸው፣ ሥነ ህይወታዊና ተፈጥሯዊ ችግሮችን የሚቋቋሙ የአዝርዕት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎች፣ የእንስሳት፣ የመስኖ፣ የእርሻ መሳሪያ ቴክኖሎጂዎች፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን የሚፈቱ ቴክኖሎጂዎች፣ በተለይም ለድርቅ ተጋላጭ ለሆኑ የዝናብ አጠርና ደረቃማ አካባቢዎች ችግሮችን የሚፈቱ ቴክኖሎጂዎች ያስፈልጉናል፡፡ አርሶ አደሮች የሚፈለጓቸው ፀረ አረምና ሌሎች ኬሚካሎች በአይነትም በአገር ውስጥ ተመርተው ሊቀርቡ ይገባል።

ትንበያዎች እንደሚያመለክቱት መጭው ዘመን በህዝብ ቁጥር መጨመርና የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ምክንያቶች የግብርና ውጤቶች ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያድግ ነው። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የግብርና ምርትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባም ግልጽ ነው፡፡ ይሁንና በተፈጥሮ ሀብት ውስንነት፣ በአካባቢ ብክለት ስጋት እና በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምክንያት ግብርናን በላቀ ሁኔታ ማሳደግ በራሱ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥና በዓለም ገበያ ሊኖር የሚችለውን ጠንካራ ውድድር ለማሸነፍ የግብርና ልማቱ ሊዘምን ይገባል። የአካባቢ እንክብካቤን ግንዛቤ ውስጥ ባስገባ መልኩ ከፍተኛ የምርት እድገት ምጣኔ ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡ ይህንን እውን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ የምርምር አቅምን በማሳደግና የተሟላ የቴክኖሎጂ አቅርቦት በማረጋገጥ ብቻ ነው።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ

 

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ፋብሪካዎች እና አርሶአደሮች በዘንድሮ የምርት ዘመን አስር ሺ ሄክታር መሬት በኮንትራት ውል የቢራ ገብስ እያለሙ እንደሚገኝ የአርሲ ዞን አስታወቀ።

በኦሮሚያ ክልል የአርሲ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አደም ቦሼ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤በአሁኑ ወቅት በአርሲ ዞን ብቻ 40 ሺ ሄክታር መሬት በቢራ ገብስ ተሸፍኗል። ከምርቱ ውስጥ 10 ሺ ሄክታር መሬት በፋብሪካዎች እና በአርሶአደሮች የኮንትራት ውል አማካኝነት እየለማ የሚገኝ ነው። በዞኑ በአንድ አመት ብቻ የቢራ ገብስ ሽፋን10 ሺ ሄክታር መሬት ጭማሪ ከማሳየቱ በላይ አርሶአደሮች ከምርቱ ከሚያገኙት ገቢ አንጻር ለማምረት ያላቸው ፍላጎት እያደገ ይገኛል።

አዳዲስ የቢራ ፋብሪካዎች በአገሪቷ መስፋፋታቸውን ተከትሎ የብቅል ገብስ ገበያው አዋጭነቱ መጨመሩን የተናገሩት አቶ አደም፤ ፋብሪካዎቹ ከገብስ አምራች አርሶአደሮች ጋር በቅድሚያ የዋጋ እና የምርት አቅርቦት ውል የሚዋዋሉ በመሆኑ በመተማመን ላይ የተመሰረተ ግብርና ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል። ፋብሪካዎቹም የተሻለ ምርት እና አቅርቦት እንዲኖር ለአርሶአደሮቹ ከምርት ሽያጩ የተወሰነውን ቅድሚያ ክፍያን ጨምሮ የተለያዩ የሙያ እና የግብአት አቅርቦት እንደሚያደርጉም አስረድተዋል። አርሶአደሮቹም ለሚያቀርቡት የብቅል ገብስ በአመረቱበት ጊዜ የሚኖረውን የዋጋ ሁኔታ ያገናዘበ የሰባት በመቶ ተጨማሪ ትርፍ ከፍለው የሚረከቡ ፋብሪካዎች በመኖራቸው የአምራቹ ገቢ እንዲጨምር ማገዙን ገልፀዋል።

የግብርና ባለሙያው አቶ አዲሱ አሸናፊ እንደሚገልጹት፤ የቢራ ገብስ አመቱን ሙሉ ተመሳሳይ ዋጋ ያለው ምርት በመሆኑ አምራቾችን የገበያ ዋጋ መቀያየር አያሰጋቸውም። የምርት ተቀባይ ፋብሪካዎችን ከቢራ ፋብሪካዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ በማደጋቸው ከአርሶአደሮች የሚጠበቀው ጥራት ያለው ምርት ማዘጋጀት ነው። በአሁኑ ወቅተ የአሰላ ብቅል ፋብሪካ ብቻ 500 ሺ ኩንታል የቢራ ገብስ በአመት ያስፈልገዋል። ፍላጎቱን ለማሟላትም ከአርሲ በተጨማሪ ወደ ሰሜን ሸዋና የተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የሚገኙ አምራቾችን እየተቀበለ ይገኛል።

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ፤ እስከ ቅርብ አመታት ድረስ በሄክታር 40 ኩንታል ያመርት የነበረው የቢራ ገብስ ሄኒከን ባስመጣው «ትራቭለር» በተሰኘው የተሻሻለ ዘር አማካኝነት በሄክታር እስከ 60 ኩንታል እየተመረተ ይገኛል። በመሆኑም አርሶአደሩ ከምርት እድገቱ ከሚገኘው ትርፍ ተጠቃሚ እንደሚሆንና በተጨማሪ በተረጋጋው የገበያ ዋጋ አማካኝነት ያለስጋት ምርቱን እንደሚያቀርብ ተረድቷል። ይህን የምርት አዋጭነት ሁኔታ በመገንዘብ በዞኑ የሚገኙ በርካታ አርሶአደሮች ወደ ብቅል ገብስ አምራችነት እየተሸጋገሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

 

ጌትነት ተስፋማርያም

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።