Items filtered by date: Friday, 01 December 2017

የቴኳንዶ ስፖርት ዶክተር ኪም ኢንዮንግ በተባሉ ደቡብ ኮሪያዊ በአገሪቱ በሚገኘው ኪኪዎን የወርልድ ቴኳንዶ ዋና መስሪያ ቤት ውስጥ መመስረቱን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ የኮሪያውን የባህል ስፖርት የሚባለው ቴኳንዶ ከሰውነት ፍልሚያ ባሻገር በውስጡ ብዙ ጥበባዊ ይዘቶችን (ስልቶችን) ያካተተ ስፖርታዊ ክንዋኔ ነው፡፡ አዕምሮንና ሰውነትን በማሰልጠን መንፈስና ስሜትን እንዲሁም ህይወትን በአግባቡ የሚያስገነዝብ የስፖርት ዓይነት እንደሆነም በዘርፉ ያሉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡

የቴኳንዶ ስፖርት ትርጓሜ በተገቢውና ጥበባዊ ስልት በተሞላበት መንገድ እግርና እጅን በመጠቀም ፀብንና ግጭትን መቆጣጠርና ማብረድ እንዲሁም ሰላምን ማስፈን ነው፡፡ ከቃላቱ ትርጉም በመነሳት የእርስ በርስ ፀብንና አለመግባባትን በማቆም የተሻለና ሰላም የሰፈነበት ዓለም ለመገንባት ያለመ መሆኑንም የስፖርቱ ጽንሰ ሃሳብ ያስተምራል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ቴኳንዶ በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ በመሆኑና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት በማግኘቱ የኦሎምፒክ ስፖርት ለመሆን በቅቷል፡፡

በስፖርቱ ውስጥ መሳተፍ ጤናማ አካልን ከማጎናፀፍ ባሻገር ማህበራዊ ግንኙነትን በማደስ እርስ በርስ መተዋወቅን፣ መቀራረብን፣ በጋራ መስራትን፣ አብሮ መኖርንና ቤተሰባዊ ፍቅርን ያጠነክራል የሚሉም አሉ፡፡

በቴኳንዶ ስፖርት የተገነባ ሰውነት ጤንነትን ለመጠበቅ ስለሚያስችል ለህክምናና ለመድኃኒት መግዣ የሚወጣን ወጪ ይቀንሳል፤ ካላስፈላጊ ውፍረትም ይታደጋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዘው የሚ መጡ በሽታዎችን ለምሳሌ የልብ፣ የስኳር፣ የደም ግፊትና የመሳሰሉትን ይከላከላል፡፡ በቂ የሆነ እንቅልፍ ለመተኛትና ድብርትን ለመከላከልም ይረዳል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ቴኳንዶ ከሩቅ ምስራቅ አካባቢ ከሚገኙ እንደ ጃፓንና ቻይና አገራት ውስጥ ከሚሰጡት የ‹‹ማርሻል አርት›› አይነቶች ጋር የሚጋራቸው ባህርያት አሉት፡፡ ይህ ማለት ግን ሙሉ በሙሉ ይመሳሰላል ማለት አይደለም ቴኳንዶ የራሱ የሆነ እንቅስቃሴ ያለው ጥበብ ነው፡፡

በቴኳንዶ ስፖርት የተለያዩ የስልጠና ዓይነቶች የሚሰጡ ሲሆን፤ የኤሮቢክስ እንቅስቃሴዎች፣ የተለያዩ ሰውነትን የማሳሳብ ስፖርቶች፣ እራስን መከላከል (ሂሶንሶል)፣ አርት(ፑምሴ)፣ ፍልሚያ (ስፓሪንግ)፣ የተመስጦ እና ትንፋሽን የመቆጣጠር፣ አዕምሮን የሚያዝናኑ ስልጠናዎች፣ የመወርወር እና የመውደቅ ቴክኒኮች፣ በይበልጥ አዕምሮአዊ እና የስነ ምግባር መርሆዎችን (Discipline) በራስ መተማመን፣ ክብርና ፍትህ እንዲሁም የሰበራ ቴክኒኮችን (ኪዩፖ)እና ሌሎችም የተለያዩ ስልጠናዎች በአንድ ላይ ተካተው ይካሄዳሉ፡፡

ባለዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው የስፖርት አይነት አገር ውስጥ በብዛት ተንሰራፍቶ ቢታይም የተደራሽነ ቱን ያህል ከተሳትፎ የሚገኘው ውጤት እምብዛም አይደለም፡፡ በአገራችን አብዛኛውን ጊዜ የተለመደው ፍልሚያ (ስፓሪንግ) ውድድር ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ከተማ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በቅርቡ ከሁለት ባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ስምምነት ሁሉንም የውድድር ዓይነቶች ያካተተ አዲስ የውድድር መድረክ አዘጋጅቷል፡፡ ስፖርቱ ላይ ያሉ እውነታዎች ንና የውድድር ገጽታውን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡትን ሦስት ግለሰቦች ሃሳብ እንደሚከተለው ተዳሷል፡፡

ለውድድሩ የፌዴሬሽኑ እንቅስቃሴ

የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኃይሉ ጉተታ ፌዴሬሽኑ ለውድድሩ እያደረገ ያለውን ዝግጅት አስመልክተው በሰጡት መረጃ፤ የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ በኢትዮጵያ ፌዴሬሽኖች መቋቋም አለባቸው ከተባለ ጊዜ ጀምሮ የተቋቋመ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ወርልድ ቴኳንዶ ሲጀመር አዲስ አበባ የቀዳሚውን ቦታ ይይዛልም ብለዋል፡፡ ከተለያየ ቦታ ቴኳንዶን የቀሰሙ ሰዎች ከተማዋ ውስጥ እንዲያድግና እንዲሰፋፋ አድርገዋል፡፡ ከዚህ ጥረት ባሻገር ግለሰቦቹ ያስፋፉት ስፖርት በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ ሁሉም ቦታ ላይ ተደራሽ ለመሆን ችሏል፡፡

በተለያዩ አገር አቀፍ ብሔራዊ ውድድሮች አዲስ አበባ በቴኳንዶ ስፖርት አመርቂ ውጤት ከሚያስመዘግቡ ከተሞች ግንባር ቀደም ስትሆን ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይም አገርን ወክለው ከሚሄዱ ስፖርተኞች መካከል በብዛት ከአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ናቸው፡፡ ይህም የስፖርቱ እንቅስቃሴ በውጤቶች ከፍ ያለ መሆኑን ያመለክታል ይላሉ፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ቀደምት እንደመሆኑ መጠን ከሌሎች ክልሎች በተሻለ ቅድሚያ ይይዛል፡፡ በስፖርቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ አሰልጣኞች ያሉበትም ነው፡፡ ስፖርቱን ለማሳደግ በብሄራዊ ደረጃ የሚሰራው ሥራ ወሳኝነት ያለው በመሆኑ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ የዓለም አቀፉን ወርልድ ቴኳንዶ ህግጋትን ተከትሎ እንዲሰራም ተደርጓል፡፡

አቶ ኃይሉ በአሁኑ ወቅት ፌዴሬሽኑ ድጎማ እያገኘ ያለው ከመንግሥት ብቻ ሲሆን፤ ከመንግሥት ድጎማ ወጥቶ ራሱን እንዲችልና ሌሎችም ክለቦች እንዲደግፍና አመርቂ ውጤት እንዲመጣ ለማድረግ ባለሃብቶችና ስፖርቱን የሚወዱ ሰዎች የሚያደርጉት አስተዋጽኦ አንድ ላይ መጣመር አለበት፡፡ የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ህጋዊ ሆነው ለሚንቀሳቀሱና በስሩ ላሉ ክለቦች የሚመለከተውን ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በተለይም በውድድር ራሳቸውን ሊያሳዩ የሚችሉበትን ዕድል እንደሚያመቻች ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ቀድሞ የነበረውን የውድድር

ልማድ ለማስቀረት

ስፖርቱ በአገር ውስጥ የውድድር መድረኮች ሲታይ የራሱ ገጽታ የነበረውና ሙሉ በሙሉ በዓለም አቀፉ የቴኳንዶ ህግጋት ያልተዳኘ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ኃይሉ፤ በዓለም አቀፉ የቴኳንዶ ህግጋት መዳኘትና ተሞክሮዎችን የግድ መውሰድና መተግበር ያስፈልጋል፡፡ «ኢትዮ ፋይት ናይት›› ተብሎ የተሰየመውና በቅርቡ የሚካሄደው አዲሱ የውድድር መድረክ የዚሁ አንድ አካል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በፊት በአገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በአዲስ አበባ ውስጥ ከአንድ ዓይነት ውድድር በላይ እንዳልተለመደ በማውሳት፤ ‹‹በቴኳንዶ ስፖርት በሌላው ዓለም ውስጥ የሚደረገው የውድድር ይዘት ምን ይመስላል? ወደ አገር ቤት ማምጣት የማይቻለ ውስ ለምድነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ተግባራዊ ለማድረግ በማስፈለጉ መርሐ ግብሩ ተነድፎ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡›› በማለትም የአዲሱን ውድድር አስፈላጊነት ያብራራሉ፡፡

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ውድድሩ አገር ቤት ያሉ ስፖርተኞች ኢንተርኔት ላይ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስሮች ከሚያገኙት ተሞክሮ ባሻገር በቀጥታ ከሌሎቹ ዓለማት የተቀዱ ስፖርታዊ ክንዋኔዎችን ለማስኬድ ይረዳቸዋል፡፡ ይህም ልምድ በስፋት ሲተገበር እውቅናው ከፍ ይላል፡፡

በአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ስር የተለያዩ ውድድሮች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ተጨማሪና አዳዲስ የውድድር መድረኮችን ማመቻቸት በማስፈለጉና ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ሊበቁ የሚችሉ ተፎካካሪዎችን ለማፍራት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹የኢትዮ ፋይት ናይት›› ውድድር እንዲካሄድ ይደረጋል፡፡ ይህም የስፖርተኞችን የውድድር ዝግጁነትና የቴኳንዶ ንቃተ ህሊናቸውን ያበረታታል ብለዋል፡፡

በአገሪቱ ከዚህ ቀደም ይካሄድ የነበረው የቴኳንዶ ስፖርት ውድድር ማዕከል ያደረገው በብዛት «ፋይት» ላይ የነበረ ሲሆን፤ በአዲሱ ‹‹ኢትዮ ፋይት ናይት›› ውድድር «ፑምሴ»፣ ሰበራ፣ «ዴሞነስትሬሽን» የመሳሰሉ የውድድር ዓይነቶች ተካተዋል፡፡ ይህም ስፖርተኞቹ እንደ ተሞክሮ እንዲወስዱት ለማድረግ የፌዴሬሽኑ ጅምር ሥራ ይሆናል፡፡

ስፖርቱን መደገፍ

ውድድሩን በአጋርነት የሚደግፉት የላፍቶ ሞል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሻውል ኃይሉ ከተመሰረተ ስምንት ዓመታትን ያስቆጠረው ላፍቶ ሞል ካተኮረባቸው ዋና ዓላማዎች አንዱ የስፖርት ኢንዱስትሪውን በልዩ ልዩ ሁነቶች ማስፋፋት ሲሆን፤ ሊያስተምሩ የሚችሉ አዳዲስ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችና ሀሳቦች ሲመጡ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ከስፖርቱ ጋር የረጅም ዓመት ዝምድና ያላቸውና የቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እስከመሆን የበቁት ዶክተር ሻውል፤ ቴኳንዶ የኦሎምፒክ ስፖርት ይሆናል ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ህልማቸው አድርገው ሲሰሩ መቆየታቸውንና ስፖርቱን ለመደገፍ ከአዲስ አበባ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር እየሰሩ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ አሁንም ‹‹ኢትዮ ፋይት ናይት››ን ውድድር በአጋርነት እንደሚደግፉ ይገልጻሉ፡፡

የቴኳንዶ ስፖርት አገሪቷ እንደ አትሌቲክሱ በዓለም መድረክ የምትታወቅበትና ስመጥር ወጣቶች የሚፈልቁበት ማድረግ ህልማቸው መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ሻውል፤ አገሪቷ የወጣት አገር እንደመሆኗ ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚሆኑና በሳል የስፖርት ክህሎት ያላቸው ወጣቶች ሊኖሩ ይገባል፡፡ ይህ ዓይነቱ የውድድር መድረክም በዚሁ የሚቋጭ ሳይሆን፤ ብዙ ተሳታፊዎችን በአገር አቀፍ፣ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ ለማብቃት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡

ዶክተር ሻውል እንደሚሉት፤ የወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ልክ እንደ ፊፋ ሁሉ እውቅና ያለው በመሆኑ ብዙ የውድድር መድረክ መኖሩ፤ የዓለም አቀፍ ግንኙነቶች እንዲዳብሩ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ‹‹ኮሪያውያን የስፖርቱን ተወዳጅነት ተረድተው በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አውጥተው ዛሬ ዓለም ላይ ከግንባር ቀደምቶቹ ተርታ ተሰልፈዋል፡፡ ዓለም ላይ በተደረጉ የኦሎምፒክ መድረኮችም በርካታ ውጤቶችን አግኝተዋል፡፡ ይህ በሥራ እንጂ በአንዴ የመጣ አይደለም፡፡ እኛም ከዚህ የምንማረው ስፖርቱን ሊያሳድጉ የሚችሉ በርካታ የውድድር መድረኮችን በማዘጋጀትና በአጋርነት ሊደግፉ የሚችሉ አካላትን መጋበዝ ያስፈልጋል፡፡

‹‹ኢትዮ ፋይት ናይት›› በማን?

እንዴትና ለምን?

የ‹‹ ኢትዮ ፋይት ናይት›› ፕሮጀክት ባለቤት ኩኪዎን ግሎባል ማስተር ዳግማዊ ወርቅነህ፤ በዚህ የስፖርት ዘርፍ ከ19ዓመታት በላይ የሰራ ሲሆን፤ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አባልና ቡድን መሪ ነበር፡፡ ከአገር ውጭ በነበረው የውድድር ተሳትፎም በርካታ ሜዳሊያዎችን ከማግኘቱ ባሻገር ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ሻምፒዮን በመሆን ሽልማቱን ያገኘ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ነው፡፡

‹‹ፕሮጀክቱን በሀሳብ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ኖርዌይ ውድድር ላይ እያለሁ ነው ያሰብኩት›› የሚለው ማስተር ዳግም፤ ‹‹በይበልጥ ውስጡ ገብቼ ሀሳቡን ወደ ተግባር መለወጥ የጀመርኩት ከአንድ ዓመት በፊት ነው፡፡›› ሲል ስለ ‹‹ኢትዮ ፋይት ናይት›› አዲስ ሀሳብ አጀማመሩ ተናግሯል፡፡ ‹‹እንዲህ ዓይነት ውድድሮች አገር ውስጥ ተደጋግመው ቢደረጉ ለተወዳዳሪዎች ትልቅ ልምድ እንደሚያስገኝ አስቤበት ነው ሃሳቡን ያመጣሁት›› በማለትም ይናገራል፡፡

ማስተር ዳግም እንደሚለው፤ ስፖርቱን ለማሳደግ ትልቁ ችግር የልምድ ማነስ ስለሆነ ‹‹ኢትዮ ፋይት ናይት›› በአንድ ጊዜ በርካታ ውድድሮችን የሚያስተናግድ በመሆኑና ከሌላው ጊዜ በተሻለ ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት ያለው በመሆኑ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ችግር ይቀርፋል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ስፖርተኞች ለማፍራትም ይረዳል፡፡ ውድድሩ ልዩ የሚያደርገው ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ቀደም ከተለመደው «ፋይት» አንድ ውድድር ባሻገር ሌሎች ውድድሮች የተካተቱበት መሆኑ ነው፡፡ በተለይ የቡድን ግጥሚያዎች ያልተለመዱ ስለሆኑ ሙሉ በሙሉ የዓለም አቀፍን ህግ ታሳቢ በማድረግ ይከናወናል፡፡

ጥቁምታ

‹‹ኢትዮ ፋይት ናይት›› ከህዳር 24 እስከ ታኀሣሥ 7 ቀን 2010.ም በአራት ኪሎ ወ...ማ እና በላፍቶ ሞል የሚደረግ ሲሆን፤ የውድድር መስፈርት ስፓሪንግ በወንድ በ54ኪሎ ግራም፣ በ58ኪሎ ግራምና በ68 ኪሎ ግራም የሚወዳደሩ ይሆናል፡፡ በዚሁ ዘርፍ ሴቶች በ4953 እና57 ኪሎ ግራም ተፋላሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የቡድን ስፓሪንግ በወንድ በ5458 እና68 ኪሎ ግራም ይወዳደራሉ፡፡ ፑምሴ በተናጠል ጀማሪ በወንድ ከ13 እስከ 17ዕድሜ ያሉ እንዲሁም በሴት ከ 13 እስከ 17ዕድሜ ያሉ ስፖርተኞች ሲወዳደሩ፤ አዋቂ በወንድ ከ 18 እስከ 30 ዕድሜ፣ በሴት ከ 18 እስከ 30የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት እንደሚወዳደሩ ታወቋል፡፡

ፑምሴ በቡድን ብዛት 3 ዕድሜ ከ 18 እስከ 30 (1 ወንድ እና ሁለት ሴት ወይም 1ሴት እና ሁለት ወንድ) ተፋላሚ ናቸው፡፡ ሰበራ በተናጠል በወንድ ከ17 እስከ 30ዕድሜ እንዲሁም ሰበራ በተናጠል በወንድ ‹‹ጢዮ አብቻጊ›› ዕድሜ 17 እስከ 30 የሚሆናቸው ይወዳደራሉ፡፡

ትርኢት በቡድን (ዴሞነስትሬሽን) ብዛት ከ3 ያላነሰ ከ8 ያልበለጠ ዕድሜ ከ17 እስከ 30 የሆናቸው ተወዳዳሪዎች የሚፋለሙ ሲሆን፤ የተጠቀሱት የዕድሜ መስፈርቶች በተሳታፊ ክለቦች ጥያቄ መሰረት እንዲሁም ለተሳታፊ ተወዳዳሪዎች ዕድል ለመስጠት በማሰብ ከተለመደው የወርልድ ቴኳንዶ ህግ መጠነኛ ማሻሻያ የተወሰደ መሆኑን የውድድር አዘጋጅ ክፍሎች ገልጸዋል፡፡

 

አዲሱ ገረመው

 

Published in ስፖርት
Friday, 01 December 2017 20:02

የራስ ከራስ አይሸሸግም

   

አጥፍቶ መሸሽ ከሰው እይታ እንጂ ከህሊና ፍርድ አያስጥልም፤

 

ኢትዮጵያ ውስጥ የብዙ ነገሮች እጥረት እንዳለ መናገር የለብኝም። የቋንቋን ድክመቶች በመጠቀም የሰውን ሀሳብ የመረዳት እጥረት ግን አሁን ወደ ጠኔነትና ወደ ጥማት ተቀይሯል። አሁን ላይ ሀሳብን የሚረዳ አዎንታዊ ሰው ማግኘት ከባድ መሆኑ ቀርቶ የማይቻል እየሆነ ነው። ስለዚህ እውነት መናገር የሚያሳፍር በአንፃሩ ነውር እንደሚያምር ጌጥ ሆኗል፡፡ እኔ ግን ዘወትራዊ ትዝብቴን አወጋለሁ፡፡ ሰሚ ቢገኝም ባይገኝም፡፡

መቼም አትታዘብ እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ መታዘቤን ከታዘባችሁ እታዘባችኋ ለሁ፡፡ ‹‹በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ›› እንዳይሆንብኝ እንጂ ያየሁትንና የሰማሁትን ለመናገር አፌም እጄም አይቆጠብም፡፡ ሰሞኑን እይታዬን ከከበቡት ነገሮች ውስጥ በድብቅ የሚሰሩ የክፋት ተግባሮች ያይላሉ፡፡

ዘመናዊነት ሲስፋፋ ተስፋ አስቆራጩ በዛ፡፡ በየጥጋ ጥጉ ተደብቀው ክፋትን የሚያመነዥኩና የተንኮልን ሀሳብ የሚያንሸራሽሩ ከህሊናቸው መሸሽ ያልቻሉ አገር በቀል ‹‹እንቶኔዎች›› ያጋጥሙኛል፡፡‹‹ እንቶኔ›› ማለቴ ስማቸውን በቀጥታ ላለመጥራት እንጂ ስም አልባ ሆነው አይደለም፡፡

ስምን በቀጥታ ስለመጥራት ሲነሳ አምባ ገነንነት ራሳቸው ላይ የወጣው የደርግ ወታደሮች ታወሱኝ፡፡ ከንቀት የመጣ ይሁን ከዝቅጠት በዚያ ዘመን ወታደሮቹ አይደለም የሰውን ስም የፈጣሪንም ስም ለመጥራት ይቸገሩ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩ አንድ አባት፤ ወታደሮቹ የታመመን ለመጠየቅ ሀኪም ቤት ገብተው ‹‹ እግዚአብሄር ወይም አላህ ይማርህ›› በማለት ፈንታ ‹‹ ለመዳን ሞክር›› ብለው ይወጡ እንደነበር በወቅቱ የታዘቡትን አጫውተውኛል፡፡

እናላችሁ እነዚህ የዚህ ዘመን ‹‹እንቶኔዎች›› ከፈጣሪና ከህሊናቸው ሳይሆን በገሀድ የሚያያቸውን የሰው ልጅ በመደበቅ ግለሰብንም ሆነ ማህበረሰቡን የሚጎዱ ተግባራትን ማከወናቸውን ተያይዘው ታል፡፡ አንተ እንዴት አየሀቸው እንዳትሉኝ! ያው አልፎ አልፎም ቢሆን እኔም የእነርሱ ተግባር ተቋዳሽ ነኛ፡፡ የአሁኑ ይባስ አላችሁ? የባሰ አለና… በሚለው ፈሊጥ እናንተም የተግባሩ ከዋኝ ናችሁ ብዬ በድፍረት ብነግራችሁስ…. አሁን እርስ በእርስ መተዛዘብ እንጀምራለን፡፡

ሰው አየኝ አላየኝ እያልን ጨለማን ተገን አድርገን በተከለከለ ቦታ ላይ ሽንት የምናንቆረቁረው ብዙዎቻችን አይደለን እንዴ፡፡ ደግሞ ጥሎብን የተቃራኒነት አባዜው ስለበረታብን ‹‹መሽናት ክልክል ነው›› የተባለበት ቦታ ላይ እኮ ነው ተግባሩን የምንፈጽመው፡፡ በየቤቶቻችን ያሉትን ደረቅ ቆሻሻዎች የሰውን ጤንነት ሊያውኩ በሚችሉ ቦታዎች ላይ የምንጥለውንም ቤት ይቁጠረን፡፡ ከበድ ሲል ደግሞ ከፈጣሪና ህሊና ውጭ ተመልካች በሌለበት በወገን ላይ ካራ የሚመዙ፣ካገኙ የሚቀሙ ካጡ በስለት ወግተው እስከወዲያኛው የሚያሰናብቱ ሰው መሳይ አውሬዎች በርክተዋል፡፡

አንድ ወዳጄ እንዳጫወተኝ እርሱ የሚኖርበት አካባቢ የውስጥ ለውስጥ መንገዱ ብርሀን አይቶት ስለማያውቅ በጨለማ በዚያ መንገድ የሚያልፉ ሰዎችን የሚዘርፉ ‹‹ሰርቆ አደሮች›› ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት እጣ ይጣጣላሉ፡፡ ይህ ማለት የተዘራፊውን ንብረት ለመከፋፈል ማን ስልኩን፣ ማን ገንዘቡን፣ ማን ልብሱን እንደሚወስድ ለመወሰን የሚያስችል ቁማር ነው፡፡ አንድ ጊዜ ስልክ ሊወስድ እጣ የደረሰው ሌባ ለተዘራፊው ቶሎ በል ስልክህን ብሎ ትእዛዝ ሲያስተላልፍ ባለ ስልኩ በጣም ከመደንገጡ የተነሳ 0911… ብሎ ቁጥሩን ነገራቸው፡፡ ይህን ሁሉ ሲያደርጉ ግን ከማንም በላይ አብጠርጥሮ የሚያያቸው ህሊናቸው አብሮአቸው ነው፡፡

ከፍየል እኩል ቅጠላ ቅጠልን ልምድ ያደረጉ የጫት ደንበኞች፣ ወሲብን ትርጉም አልባ አድርገው በድብቅ ጾታዊ ጥቃትን የሚያደርሱ … በጤፍ ላይ ጀሶ እየቀላቀሉ የሚነግዱ፣ ቅቤና ሙዙን አንድ ላይ አድርገው ያዋሀዱ… እነዚህ ሁሉ ሽሽታቸው ከሰው ቢሆንም ከህሊና ፍርድ ማምለጥ አይችሉም፡፡

ለመሆኑ ተሸፋፍነው ቢተኙ ገልጦ ማየት የሚችል አምላክ መኖሩን ረስተን ይሆን? ካልረሳን ደግሞ ሰውን ሳይሆን ህሊናችንን መፍራት እንጀምራ፡፡ ሰዎች ከሚወቅሱን የከፋ እኮ ህሊናችን የሚሸነቁጠን ያማል፡፡ በህሊናው የሚመራ ግለሰብ መሪና አዛዥ አያሻም፡፡ ህሊናዬ የኔ ንጉስ ነውና እምቢተኛ አልሆንበትም፣ ህሊናዬን እታዘዘዋለሁ የሚል ስብእና ይኑረን፡፡

ነገሬን ለማዋዛት አንዲት ትንሽ መንደርን የሚያስተዳድሩ መሪ የመንደራቸውን እድገት ለማፋጠን ከማሰብ የአካባቢውን ማህበረሰብ ስብሰባ ይጠራሉ፡፡ መሪው ህዝቡን በአትኩሮት ከተመለከቱ በኋላ ‹‹እነሆ ዛሬ እዚህ የመሰባበሰባችን ምስጢር አንድና አንድ ነው፡፡ ለረጅም አመታት የደኸየችና በችግር የኖረች መንደራችንን ተባብረን ማቅናት ይኖርብናል፡፡ ለለውጣችን ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ትትክለኛው ጊዜ ደግሞ አሁን ነው፡፡ ዓለም ቀድሞናል፡፡ እኛ ግን ተቀምጠናል፡፡ የዓለም ህዝብ በሳይንስ ረቅቋል፡፡ እኛ ግን ቁልቁል እየተጓዝን ወሬ እያቦካን ድህነትን እንጋግራለን፡፡ትላንት ባረስንበት በሬ እያረስን እኛነታችንን ረስተን የነጭ ቲፎዞ ሆነናል፡፡ ሮጠን ቀደምናቸው ቆመን ጠበቅናቸው ጥለውን አለፉ ሆኗል ተረታችን፡፡

እንግዲህ ቁጭቱ ይቆየንና ጥረቱ ይቀጥል፡፡ የተሻለ ህይወት መኖር ይኖርብናል፡፡ ለመጪው ትውልድ የጸዳና ያልቆሸሸ ቅርስ ማውረስ ይጠበቅብናል፡፡ እናም በዛሬዋ ምሽት በዚህች መንደር የምትኖሩ ሁሉ ፊት ለፊታችሁ የምትመለከቱት ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ የተቀበረ ረጅም በርሜል አለ ፡፡ እዚህ በርሜል ውስጥም እያንዳንዳችሁ አንድ አንድ ጣሳ ወተት በማምጣት ትጨምራላችሁ፡፡ በወተቱም ሽያጭ ያልተለወጠች መንደራችንን እንለውጣለን፡፡ ይህ እያዳንዳችሁ ምን ያህል ለትውልድ አሳቢ እንደሆናችሁ ለመንደራችሁም ያላችሁን ፍቅርና ተቆርቋሪነት ለማወቅ ያቀረብኩት የመጀመሪያ ፈተናዬ ነው፡፡

እናም ለህሊናችሁ ስትሉ ሰው እያየኝ ሳይሆን ፈጣሪ ያየኛል ብላችሁ ፈጽሙት፡፡ ወተቱን አምጥታችሁ እዚህ ጉድጓድ ውስጥ ስትጨምሩ ማንም ማንንም እንዳያይ! እያንዳንዳችሁ ወተቱን እዚህ ጉድጓድ ውስጥ የምትደፉት በዛሬዋ ምሽት ብቻ ይሆናል፡፡ እኔም በማለዳ ወጥቼ የሆነውን አያለሁ፡፡›› ብለው የመንደሩን ነዋሪዎች ተሰናበቱ፡፡

የመንደሩ ነዋሪዎችም የመሪያቸውን ትእዛዝ በየግላቸው እያሰላሰሉ ወደየመኖሪያ ቤታቸው አመሩ፡፡ ሁሉም ተግባሩን በየጓዳው ቀጠለ፡፡ ከነዋሪዎቹ አንዱም በአንድ ትልቅ ጣሳ ወተቱን ሞልቶ ቆመና ፈንጠር ፈንጠር እያለ መኖሪያ ቤቱን በጥንቃቄ ፈተሸ፡፡ ጥቂት አሰበና… ‹‹ግን ለማን አባቱ ብዬ! ለምድረ ምናምንቴማ ሁሉ ወተቴን አልሰጥም፡፡ ለህሊና ብሎ ሽርደዳና ሽወዳ አይዋጥልኝም፡፡ ጣሳዬን… በውሀዬ ሞልቼ… ከተባለው ጉድጓድ ውስጥ እጨምራለሁ እንጂ ወተትማ እንዳማራቸው ይቅር፡፡ ደግሞም እኮ ሌሎቹ ጅላ ጅል የአካባቢያችን ነዋሪዎች ወተታቸውን ይዘው ስለሚወጡና ጉድጓዱ ውስጥ ስለሚጨምሩ እኔ ውሀዬን ብጨምር ወተት አምጪው ስለሚበዛ የእኔ ውሃ መጨመር በምንም ሁኔታ ሊታወቅ አይችልም፡፡›› በማለት እንደፎከረ በዚያች ምሽት ውሀውን በጣሳ ሞልቶ ጉድጓዱ ውስጥ ጨመረና ተመለሰ፡፡

ከዚያች ሰአት ጀምሮ ህሊናው ራሱን ይደበድበው ጀመር፡፡ መኖሪያ ቤቱ እንደደረሰም ከህሊናው እየተቧቀሰ ‹‹የት አባታቸው ሰራሁላ ቸው፡፡ አዳሜ … ወተቱን ሲያመላልስ እኔ ሆዬ… ውሀዬን አንቆረቆርኩላቸው! ነፈዝ ሁላ!›› ብሎ መኝታው ላይ ወጥቶ ተከናንቦ ተኛ፡፡

በዚያች ምሽት አካሉ እንጂ ህሊናው ራቁቱን ነበር፡፡ መንጋት አይቀር ነገር ነጋ፡፡ የአካባቢው መሪም ማልደው ወደ ጉድጓዱ ይደርሱና የሆነውን ይመለከታሉ፡፡ ወዲያው በሁለት እጃቸው አፋቸውን አፍነው ፈጠጡ፡፡ ማንም ከእንቅልፍ አልተነሳም ነበር፡፡ አዳሜ ከነ ቆሻሻው ሀሳቡን ጥሎ ያንኮራፋል፡፡ መሪውም ወዲያውኑ የመንደራቸውን ኋላ የመቅረት ምስጢር ተገነዘቡ፡፡ በሆነውም ነገር ክፉኛ አዘኑ፡፡ ከዚያ ሁሉ ህዝብ ውስጥ ብቻቸውን ናቸው፡፡ መሪው ደግመው ወደ ጉድጓዱ ተመለከቱ፡፡ ለወተት ማጠራቀሚያነት የተዘጋጀው ጉድጓድ አፉ ድረስ ጢም ብሎ ሞልቷል፡፡ ነገር ግን የጉድጓዱ ሙላት አያስደ ስትም፡፡ የጉድጓዱ ሙላት በመሪው አይን ጉድለት ነበረው፡፡ ለምን እንዴት ብለው ከጠየቁ … ጉድጓዱን የሞላው ወተት ሳይሆን ውሀ ነበርና ነው፡፡ ለካስ የመንደሩ ነዋሪ በሙሉ እንደዛ ማን ያየኛል ውሀዬን አፍስሼ ብመጣ እንዳለውና ውሀውን ጉድጓድ ውስጥ ጨምሮ እንደተመለሰው ግለሰብ ሁሉም ማን ያየኛ በሚል ውሀቸውን ሲጨምሩ ነበር ያደሩት፡፡ አይ ዝቅጠት!

አእምሯችንን የትራስ እራት ብቻ አድርገነዋል። ህሊናውን የራሱ አለቃ ማድረግ የቻለ ለሰው ሲል አይሰራም፡፡ የራሱንም ከራሱ አይሸሽግም፡፡ የራስ ከራስ ሊደበቅ አይችልም፡፡ በህሊናው ላይ የሚያምጽ በመኖሩ ላይ አድማ የወጣ ሰው ነው፡፡ ህሊናችንን ስንታዘዝ ህይወታችንን ከህጸጾች እንታደጋለን፡፡ ዘወትር ከህሊናው ጋር የቅርብ ወዳጅነትን የሚመሰርት ሰው ራሱን እንጂ ሌሎችን እያየ አይኖርም፡፡ እኛ መሆን ያቃተን እኮ ሀይላችንን በሙሉ ራሳችንን በመሆን ሳይሆን ሌሎችን በመምሰል እየጨረስነው ነው፡፡ በህይወቱ ፈቀቅ ማለት የፈለገ ሰው በኑረቱ ረቀቅ ማለት ይገባዋል፡፡

ከህሊና ፍርድ እንደማናመልጥ እየተረዳን ከሰው ተደብቀን ነገር ግን ከህሊናችን ተፋጥጠን ነውራችንን እንከምራለን፡፡ ከሰው እይታ ሳይሆን ከራስ ህሊና ራስን መደበቅ አይከብድምን?

 

አዲሱ ገረመው

 

 

Published in መዝናኛ

ባሳለፍነው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ በምርምርና ፈጠራ ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ የመዋቅር ሽግግር ሊያመጡ የሚችሉ አመላካች የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች ሰርተዋል ተብለው በውድድር ለተመረጡ የፈጠራ ባለሙያዎች ሽልማት አበርክተው የኢትዮጵያን «የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍን» በተመለከተ ያስቀመጡትን የመንግስት አቋም በዚህ አምዳችን ማቅረባችን ይታወሳል። መንግስትም ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠቱን፤ ያለ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የአገሪቷን ኢኮኖሚ ማዘመንም ሆነ ስልጣኔን ማስፋፋት እንደማይቻል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በዚህ የሽልማት ስነስርአት ላይ የተገኙ ባለድርሻ አካላት አስተያየታቸውን ሲሰጡ ተደምጠዋል።

ለስምንተኛ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ የሳይንስ የቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን የሽልማት ስነ ስርአት ላይ በሂሳብ እና በሳይንስ ትምህርት እንዲሁም በአገር በቀል ፈጠራና ኢኖቬሽን ስራ የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ናቸው የእውቅና እና የማበረታቻ ሽልማት የተበረከተላቸው።

አቶ አብዱ አህመድ ከተሸላሚዎቹ መካከል በአማራ ክልል በደሴ የከተማ አስተዳደር የሆጤ ትምህርት ቤት የፊዚክስ የትምህርት ክፍል መምህር ናቸው። ሽልማቱን እንዲያገኙ ምክንያት የሆናቸው ከተፈጥሮ እፅዋት የሰሩት መድሀኒትነት ያለው ሳሙና ነው። ከነጭ ሽንኩርት፣ከእንዶድ፣ከአልጌ፣ከእሬት እና ሌሎችንም መድሀኒትነት ያላቸው እፅዋትን በመቀመም ሳሙናውን ማምረት ችለዋል። ይህ ሳሙና በፈሳሽ እና በጠጣር መልክ የተሰራ ሲሆን፤ ሳሙናው ለፎረፎር፣ ለቋቁቻ እንዲሁም ለመሰል የቆዳ በሽታዎች ያገለግላል። ከዚህም ሌላ አሲድነቱን በመቀነስ በሰውነት ላይ የሚታየውን ድርቀት እና ምቾት የሚነሳ ወዝ ማጣት እንደሚያስቀር ነው የፈጠራ ባለሙያው የሚናገሩት።

በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አማካኝነት በስምንተኛው አገር አቀፍ የሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን ሽልማት አሸናፊዎች መካከል አንዱ በመሆኔ አሁን ከሰራሁት የፈጠራ ስራ የተሻለ በቀጣይ በርካታ ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂና የምርምር ውጤቶችን እንድሰራ እገዛ ያደርግልኛል ሲሉ ለዝግጀት ክፍላችን ሀሳባቸውን አካፍለውናል። በሆጤ ትምህርት ቤት የሚያስተምሯቸውን ተማሪዎች በማስተባበርም የተሻለ የፈጠራ ስራ ለመከወን ጥረት እንደሚያደርጉ በመግለፅ ለምርምር ውጤቶች ያላቸውን መልካም እሳቤ ይናገራሉ።

ሌላኛው ተሸላሚ ዶክተር ሳሙኤል ሳህለ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በባይሎጂ የትምህርት ክፍል በመምህርነት እና በተመራማሪነት ይሰራሉ። ከሁለት ተባባሪ ተማሪዎቻቸው ጋር በመሆን «ዳጉሳን ለቢራ መጥመቂያ» ለማዋል ባደረጉት ጥረት የተሻለ ውጤትን አስመዝግበዋል። በዚህም የወርቅ ሜዳሊያ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ አማካኝነት በስምንተኛው አገር አቀፍ የሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን ሽልማት ከጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

«አብዛኛውን ጊዜ የቢራ መጥመቂያ ገብስ ከውጪ በከፍተኛ የምንዛሬ ዋጋ ይመጣል» የሚሉት ተመራማሪው፤ ይህንን ለማስቀረት እና አዲስ አማራጭ ምርት ወደገበያው ለማቅረብ በዳጉሳ እህል ላይ የሙከራ ጥናት ማድረጋቸውን ይገልፃሉ። በኢትዮጵያ አንዳንድ ቦታዎች የዳጉሳን ምርት ለጠላ መጥመቂያ እና ለተለያዩ የመጠጥ አይነቶች ጥቅም ላይ ይውላል። ከዚህ መነሻም ይህን እህል ወደ ቢራ መጥመቂያነት ለመቀየር የተደረገው ሙከራ ውጤታማ ሊሆን ችሏል። ለዚሁ ግልጋሎት የሚውል የዳጉሳ የዘር አይነቶችም በምርምር ሂደቱ ላይ ለመለየት ተችሏል።ውጤቱ ከቢራ በተጨማሪ አልኮል ተጠቃሚ ላልሆኑ ሰዎች የሚውል መጠጥ ከዳጉሳ ለማምረት ያስችላል። በዚህ የሙከራ ጥናት ላይ ከዳጉሳ የሚመረተው ቢራ በጣዕምም ሆነ በመልክ እስካሁን ካሉት የተሻለ እንደሆነ ነው ተመራማሪው የሚገልፁት።

«በምርምሩ የተገኘው ውጤት አመርቂ በመሆኑ በርካታ አካላት ከኛ ጋር ለመስራት ጥያቄ አቅርበውልናል» የሚሉት ዶክተር ሳሙኤል፤ ሽልማቱን በማግኘታቸው ለቀጣይ ስራቸው ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርላቸው ይናገራሉ። ቀደም ሲል በርካታ የምርምር ስራዎችን መስራታቸውን በመግለፅም ተከታታይ እና ችግር ፈቺ የሆኑ ሳይንሳዊ ምርምሮችን ለመስራት የተደረገላቸው ማበረታቻ እንደሚያግዛቸው ይናገራሉ። በግብርናው ዘርፍ ምርትን ለማሳደግ የሚደረጉ ጥረቶች ላይ የበኩላቸውን ለማበርከት ቁርጠኝነት እንዳላቸውም ይገልፃሉ። አብዛኛውን ጊዜ በፈጠራ ባለሙያዎች የሚሰሩ ስራዎች ታይተው ተግባር ላይ ሳይውሉ እንደሚጠፉ የሚገልፁት ተመራማሪው፤ ይህ እንዳይከሰት መንግስትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል በማለት የግል አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። በአሁኑ ወቅት መንግስት ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት የሚያበረታታ መሆኑን በመግለፅም አስተያየታቸውን ይቋጫሉ።

ገብረመድህን ተክላይ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪና የትግራይ ክልል ነዋሪ ሲሆን፤ከአካባቢው ችግር ተነስቶ የጤፍ መፍጫና ቆሻሻ መለያ፣ የእንጨት መቁረጫ እና የወተት መናጫን መስራት ችሏል። በዚህም በስምንተኛው አገር አቀፍ የሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን ሽልማት በጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ ከመሰል ጓደኞቹ ጋር የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።

«እነዚህን የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች ለመስራት ያስቻለኝ በአካባቢዬ ዋንኛ ችግሮች በመሆናቸው ነው» የሚለው ገብረመድህን፤ ከዚህ በመነሳት የማህበረሰቡን ድካም የሚያቃልል የቴክኖሎጂ ውጤት ማበርከቱን ይገልፃል። ስራዎቹ በአገር አቀፍ ደረጃ ተወዳድረው በማሸነፋቸውም ትልቅ ደስታና ኩራት እንዲሰማው እንዳደረገውም ገልጿል። ይህ ማበረታቻም ወደፊት ለሚሰራቸው የፈጠራ ውጤቶች የሞራል ስንቅ እንደሚሆነውም ነው የሚገልፀው። «የሽልማት ትልቅና ትንሽ የለውም» የሚለው ወጣቱ፤ ዋናው ጉዳይ የፈጠራ ስራ ለሚሰራ ሰው እውቅና ማግኘት መቻሉ ነው ይላል። ወደፊት በተሻለ ስራ ጠብቁኝ እያለ አስተያየቱን ይቋጫል።

ተማሪ አስራት እንዳለ በበቆጂ ፕሪፓራቶሪ ትምህርት ቤት የ12ተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፤በሰራው አመርቂ የፈጠራ ስራ በስምንተኛው አገር አቀፍ የሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን ሽልማት ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።

«የፀሀይ ሀይልን በመጠቀም የሰውን አሻራ ለመለየት የሚችል መሳሪያ፣ ሀይል ቆጣቢ የእንጨት መሰንጠቂያ ሰርቻለሁ። በተመሳሳይ የፀሀይ ብርሀንን በመጠቀም ሀይል የሚያመነጭ መሳሪያም ፈጥሬያለሁ» የሚለው ተማሪ አስራት፤ በርካታ የፈጠራ ስራዎች እንዳሉት ይገልፃል። በዚህም ለሽልማት ታጭቶ አሸናፊ እንደሆነ ይናገራል። የሰራቸው ማሽኖች የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር በመፍታት ላይ እንደሆኑ እና የልፋቱን ውጤት ማየት እንደቻለም ያስረዳል።

ተማሪ አስራት በሽልማቱ መበረታታቱን እና ለተሻለ ስራ መነሳሳቱን ያስረዳል። ለሌሎች አርአያ መሆኑ ደስተኛ እንዳደረገው እና በዚህ ተግባሩ እንደሚቀጥልበትም ነው የሚናገረው። የፈጠራ ባለሙያዎች በልዩ መልኩ ትኩረት ሊሰጣቸው እና ሊደገፉ እንዲሁም መብቶቻቸው ሊከበሩ ይገባል የሚል መልክትም አለው።

የፍቼ ከተማ ነዋሪ የሆነው ተማሪ ገመቺሳ አየለ ሌላኛው የፈጠራ ባለሙያ ሲሆን፤ የሰራው ፕሮጀክት በከተማም ሆነ በገጠር ከተማዎች ማህበረሰቡ የሚተክላቸውን የጓሮ አትክልቶች በአስፈላጊው ጊዜ ውሃ የማጠጣት ስራ የሚያከናውን ማሽን ነው። ማሽኑ ያለምንም እርዳታ በአፈር ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመገምገም በአስፈላጊው ሰአት እና መጠን ውሀውን የማጠጣት ስራ ያከናውናል። በዚህ ፕሮጀክት የፈጠራ ባለሙያው በስምንተኛው አገር አቀፍ የሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን ሽልማት በጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ የብር ሜዳሊያ ተበርክቶለታል።

«የሽልማት ስነ ስርአቱ በጣም ደስ የሚል ስሜት የሚፈጥር እና አበረታች ነው» የሚለው ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ፤ አብዛኛውን የሚሰሩ ስራዎች ግን ተደጋጋሚ እና አዲስ አይደሉም የሚል ትዝብት እንዳለው ይገልፃል። አዲስ ያልሆነውን አሻሽሎ መስራት ከተቻለ መልካም ነው። ከዚህም ሌላ የምንሰራቸው የፈጠራ ስራዎች ችግሮቻችንን መፍታት የሚችሉ መሆን አለባቸው የሚል እምነት እንዳለው ያስረዳል። ይህ ካልሆነ ግን ቴክኖሎጂው አዲስ ነገር እንደተፈጠረ ላይቆጠር ይችላል የሚል አመለካከት አለው።

በዚህ ውድድር ላይ ተቀባይነት ባያገኝም መስማት የተሳናቸውን ሰዎች የሚያግዝ ቴክኖሎጂ እንደሰራና በሚቀጥለው ጊዜ አሻሽሎ ለውድድር እንደሚያቀርበው ገልጿል። ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ፤ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ውስጥ የላቀ አበርክቶ እንዲኖረው በጥረት ለመስራት ተስፋ እንዳደረበት ይገልፃል።

በስምንተኛው አገር አቀፍ የሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን ሽልማት ላይ በርከት ያሉት ተሳታፊ ታዳጊዎችና ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። ይህ የሚያመለክተው ደግሞ በዘርፉ የተሻለ እመርታ የሚመዘገብበት አመላካች ተስፋ መኖሩን ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ለወጣት እና ታዳጊ ተመራማሪዎች ልዩ ትኩረት እንደሰጠ እየገለፀ ይገኛል።

አገሪቷ ከግብርና መርህ ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መርህ ኢኮኖሚ እያደረገች ያለው ሽግግር ስኬታማ እንዲሆን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጉዞዬን ከእርምጃ ወደ እሩጫ ቀይሬያለሁ እያለ ይገኛል።መስሪያ ቤቱ የሰው ሀብት ልማቱ ላይ አትኩሮ ከመስራቱ ባሻገር በዘርፉ አስፈላጊ የሆኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እያካሄደ መሆኑን ገልጿል። በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ ልዩ ተሰጥዎ ያላቸውን ህፃናት የሚያወጣ ማእከል ለመገንባት ዝግጅቱን አጠናቅቋል። ከዚህም ሌላ በርከት ያሉ የስልጠና እና የቴክኖሎጂ ማእከሎችን ለማቋቋም እየሰራሁ እገኛለሁ ብሏል። የዝግጅት ክፍላችን በቀጣይ ሳምንት በዘርፉ ሊሰሩ የታቀዱ ተግባራትን በዝርዝር የሚዳስስ ይሆናል።

 

ዳግም ከበደ

Published in ማህበራዊ

 

ኢትዮጵያ 30በመቶ የሚሆነው ህዝቧ ወጣት እንደሆነ ይነገራል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ወጣት እንደሚኖር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡በወጣት የተገነባች ሀገር ደግሞ ልማቷ የተፋጠነና የዕድገት ግስጋሴዋም ያልተቋረጠ ይሆናል፡፡በዚሁ መሠረት በልማት፣ በሰላምና በዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ እንዲሁም በማህበራዊ አገልግሎቶች እና በኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ ወጣቱን በማሳተፍ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ወጣቱ ከልማት እና ከእድገት ወደኃላ በሚጎትቱ ነገሮች ላይ በመሳተፍም የጥፋት ኃይል የሆነበት አጋጣሚም ተከስቷል፡፡

2009.. በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያና በአንዳንድ የሀገሪቷ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ሁከትና ግርግር ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሁከትና ግርግሩ የወደሙት ልማቶችና ሀብቶች ሀገራቸውን በሚወዱ ዜጎች የተፈፀመ ነው ብሎ ለማመን እስከሚከብድ ድረስ ጥያቄ የፈጠረ ድርጊት ነበር፡፡ሀገሩን ወደተሻለ ደረጃ ያደርሳታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ወጣት በዚህ ድርጊት የተሳተፈበት ምክንያት አሳማኝ እንዳልሆነም ብዙዎች ይገልፃሉ፡፡

ወጣቶች የተለያዩ ጥያቄዎቻቸውን የሚፈቱ ባቸው፣ ማህበራዊ አገልግሎታቸውን የሚያጠናክ ሩበት፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚያጎ ለብቱበት እንዲሁም የፖለቲካ ተሳትፎን የሚለማመዱ በት የተለያዩ አደረጃጀቶች በሀገሪቷ ተመቻችተውላ ቸዋል፡፡ ነገሮችን በአደረጃጀቶች መቆጣጠርና መከላከል ለምን አልተቻለም? ወደፊትስ ለሀገሩ አሳቢ የሆነ ወጣት እንዲፈጠር ምን እየተሰራ ነው? በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበርን፣የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤትን አነጋግረናል፡፡

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይሁኔ መሐመድ ሁከትና ግርግሩ በአዲስ አበባ ከተማ ባይከሰትም ነገ ለሚሆነው ነገር ዋስትና እንዳልሆነና በሌሎች አካባቢ የተፈጠረው ሁከትና ግርግር እንደሚያሳስበው ይናገራል፡፡«ወጣቱ ባልተገባ ድርጊት ውስጥ ሲሳተፍ እውቀት የጎደለውና ማመዛዘን ያቃተው ነው ብዬ አልገምት፡፡ ምክንያቶቹን በጥልቀት ማየት እና በጥናት መደገፍም አለበት»ሲልም ይገልፃል፡፡አቶ ይሁኔ እንዳለው ሀገር ወዳድ እና ተቆርቋሪ ዜጋ ለማፍራት ከታች በትምህርት ቤት ብዙ መሠራት አለበት፡፡ በኪነ ጥበብ ዘርፉ የሚቀርቡ ዘፈኖችም መቃኘት አለባቸው፡፡በአንዳንድ የሙዚቃ ባለሙያዎች የሚተላለፉት መልዕክቶች ወጣቱን በቀላሉ የሚቀሰቅሱ እና ወደ አንድ አቅጣጫ የሚወስዱ በመሆናቸው በትኩረት መታየት አለባቸው፡፡ የዘፈኑን መልዕክት ከተረዱ በኃላ በሙዚቃው መጫወታቸው የሚቆጫቸው እንዳሉም ተናግሯል፡፡ ከሀገራዊው ይልቅ ክልላዊ አስተሳሰቦችን የሚያጎሉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን መታዘቡንም ገልጿል፡፡

ወጣት ይሁኔ እንዳለው በወጣት ማህበሩ ከተደራጁትም ሆነ በአባልነት ካልታቀፉት ማህበሩ የተገነዘበው ወጣቱ የተጠቃሚነት ጥያቄው ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡«ሀገሪቷ እያደገች ነው እኔም የእድገቷ ተቋዳሽ መሆን አለብኝ»የሚለው በዋናነት ይነሳል፡፡ በየአመቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቆ የሚወጣውን የተማረ ኃይል የሚያስተና ግድ ተቋም መፍጠር አለመቻል፣የወጣቱ የሱስ ተጋላጭነትና በመጤ ባህል መያዝ ሀገራዊ ስሜቱ ላይ ተፅዕኖ እንዳለው ወጣቱ በተደጋጋሚ ከሚያነሳቸው ጥያቄ ውስጥ ይጠቀሳል፡፡ጥያቄው ተገቢነት ያለው ቢሆንም ባልተገባና ሁከት በመፍጠር ሳይሆን በተደራጀና አግባብ ባለው መንገድ መቅረብ አለበት፡፡ጥያቄውን መወርወር ብቻ ሳይሆን ሀገሩ ከእርሱም እንደምትጠብቅ መረዳት አለበት፡፡እርሱ እንዳለው በማህበር መደራጀቱ ጥያቄዎችን ለማቅረብና የመንግሥትን ጆሮ ለማግኘት ያግዛል፡፡የወጣት ማህበሩ ተደራሽነቱን ለማስፋት በከተማዋ አስተዳደር በሚገኙ 117ወረዳዎች ጽህፈት ቤት ከፍቶ እየሰራ ሲሆን፤ በማህበሩ ያልታቀፉትንም በሚያከናው ናቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ ይገኛል፡፡ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እንዲሁም ሙያዊና የተለያዩ ድጋፎችን ለማግኘት ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማትና ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በጋራ እንደሚሰራም አቶ ይሁኔ አስረድቷል፡፡

«ወጣቱን ወክለው ሊጉን ጨምሮ የተደራጁ የተለያዩ አደረጃጀቶች ወጣቱን የመፍትሄው አካል በማድረግ አሁን እያደረጉ ካሉት እንቅስቃሴ በላይ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ መስራት ይጠበቅባቸዋል» ያለው የአዲስ አበባ ወጣቶች ሊግ ሊቀ መንበር አቶ ጥበቡ በቀለ በበኩሉ የወጣቱን ስብዕና ለመገንባት እንዲሁም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነቱን ለማጎልበት ሥራዎች ቢሰሩም በቂ እንዳልሆኑ ያምናል፡፡ወጣቱ አዕምሮውን የሚያድስበትና አካሉንም የሚያጎለብትበት የስፖርት ማዘወተሪያና ሌሎችም ማህበራዊ አገልግሎትን የማጠናከር ሥራዎች ይቀራሉ፡፡የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን ደግሞ የሥራ ዕድል ፈጠራውን የገንዘብ ድጋፍና የሥራ ቦታን በማመቻቸት በሚሰማሩበት ቦታ ውጤታማ እንዲሆኑ በሙያ ክህሎት በማብቃት፣ የገበያ ትስስር በመፍጠር እንዲሁም በሥራ ላይ ችግር ሲያጋጥማቸው ተከታትሎ በመፍታት ያልተቋረጠ እገዛ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ወጣቱ በሥራ ሲጠመድ በሀገር ግንባታ ላይ አዎንታዊ የሆነ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ጎን ለጎንም ከአስተሳሰብ እና ከአመለካከት ክፍተት የሚመነጨውን ችግር በጋራ መድረክ በመነጋገርና በመወያየት የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት የየአደረጃጀቶቹ የቤት ሥራ እንደሆነም ተናግሯል፡፡

በአደረጃጀቶች ውስጥ ከሚገኘው ወጣት ይልቅ በአባልነት ያልተሳተፈው እንደሚበልጥ የገለፀው አቶ ጥበቡ የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩም በማህበር ተደራጅቶ መንቀሳቀሱ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ እና በተለይም ወጣቱ በልማት ቡድን ተደራጀቶ ቢሰራ ከራሱ አልፎ ቤተሰቡን፣አካባቢውንና ሀገሩን እንደሚጠቅም አመልክቷል፡፡ሊጉ የኢህአዴግን ፕሮግራምና ዓላማ የተቀበሉ አባላትን ይዞ የሚንቀሳቀስ ቢሆንም ለአዲስ አበባ ወጣቶች ተጠቃሚነት እንደሚሰራም ገልጿል፡፡

በሥሩ 8.7ሚሊዮን ወጣቶች፣8 ያህል የወጣት አደረጃጀቶችና ማህበራትን ይዞ የሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ወጣቱ በያለበት አካባቢ የልማት ተሳትፎውን በማጎልበት ለውጥ እንዲያመጣ ከፌዴራልና ከክልል ከሚመለከ ታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሙሐዲን ናስር ያስረዳል፡፡እርሱ እንዳለው ወጣቱ ባለበት አካባቢ ውጤታማ ለመሆን ጥረት ከማድረግ የለማ አካባቢን የመፈለግ ዝንባሌ ይስተዋላል፡፡ በመሆኑም በተወሰኑ ከተሞች ላይ ፍሰቱ ከፍተኛ ነው፡፡ይህ ደግሞ ለሁሉም ሥራ ለመፍጠር ተግዳሮት ይሆናል፡፡የአካባቢን ሀብት የመጠቀም ባህልን በማዳበር የወጣቱን የሥራ ዕድል ጥያቄም ሆነ የልማት ተጠቃሚነት ችግር መቅረፍ ይቻላል፡፡ ፌዴሬሽኑ በክልል ላይ ያሉ አደረጃጀቶች የአካባቢያቸውን ወጣቶች ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያከናውኗቸውን እንቅስቃሴዎች በመቃኘት መልካም ተሞክሮ ያላቸው ወደ ሌሎች የሚሰፋበትን መንገድ እያመቻቸ ይገኛል፡፡በአሁኑ ጊዜም በወጣቶች ተጠቃሚነት ላይ ከሰሩት ክልሎች ትግራይ፣ ደቡብ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የተሻሉ ናቸው፡፡ ታዳጊ ክልሎች ላይ ደግሞ እንቅስቃሴው ደካማ ነው፡፡ የወጣት አደረጃጀ ቶችን መፍጠር ላይ ክፍተት አለባቸው፡፡ በተሻለ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ ቢሆኑም የበለጠ ተጠናክረው ውጤታማ የሆነ ሥራ እንዲሰሩ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ አደረጃጀቶቹ በጤና፣ በትምህርትና በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ መስራት ቢፈልጉ በዘርፉ የሚሰሩ ተቋማት ድጋፍ ያስፈልጋ ቸዋል፡፡ በሌሎችም ተግባራቶቻቸው የሚያግዛቸው ከተገኘ የወጣቱ ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እየተፈታ ታታሪና ጠንካራ የሆነ ወጣት መፍጠር ይቻላል፡፡

የወጣቶች አደረጃጀት መኖር የተለያዩ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ የገለፀው ኃላፊው በአደረጃጀቶቹ አቅም የሚፈቱት ወዲያው መፍትሄ እንዲያገኙ እንደሚያስችልና ከአደረጃጀቶቹ አቅም በላይ የሆኑት ደግሞ በተደራጀ መልኩ ለሚመለከተው አካል ቀርበው ምላሽ ለማግኘት እንደሚያስችል አስረድቷል፡፡ የአደረጃጀቶችን ጥቅምና አስፈላጊነት ግንዛቤ በመፍጠር በኩልም መሰራት እንዳለበት ያምናል፡፡«ወጣቱም እራሱ ያልተሳተፈበትንና ያልሰራውን ዕድገት መጠበቅ የለበትም፡፡ከሌሎች ከለሙና ካደጉ ሀገራት ጋር ማወዳደርም የለበትም፡፡ ሀገሪቷ የጎደላትን በመሙላት እየተከናወነ ባለው የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት የሚጠበቅበትን ማበርከት አለበት»በማለት ወጣቱ በያገባኛል መንፈስ እንዲንቀሳቀስ አቶ ሙሐዲን ያሳስባል፡፡በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ግልጽ ሆኖ መቅረብ መጀመሩ መልካም እንደሆነም ተናግሯል፡፡ሆኖም ግን መንግሥት ችግሮች ሲኖሩ ብቻ ሳይሆን፤ ከወጣቱ ጋር የሚገናኝበት የውይይት ጊዜ እንዲኖር ማመቻቸት ወጣቱ ጉልበቱንና አዕምሮውን አቀናጅቶ ለሀገሩ ልማት የሚያውልና ሀገሩን የሚወድ ወጣት ለመገንባት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚያግዝ አስረድቷል፡፡

 

ለምለም መንግሥቱ

 

 

Published in ፖለቲካ

ኢንቨስትመንት በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ውስጥ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ግዙፍ የፋይናንስ አቅም ያላቸው ባለሀብቶች ገንዘባቸውን በስራ ላይ በማዋል በአገር ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ አሻራ እንዲያሳርፉ እድል የሚሰጠው ይህ ዘርፍ፣ በጥንቃቄ የተቀመሩ ፖሊሲዎችንና መመሪያዎችንም ይፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች አገር ከመሆኗም በተጨማሪ ሰፊ የሆነ አምራች የሰው ኃይል ባለቤት በመሆኗ እምቅ የሆነ የኢንቨስትመንት አቅም አላት፡፡ ይሁን እንጂ ይህን አቅም በሚገባ በተግባር ላይ ለማዋል የሚያስችል ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድሎች ስላልነበሩ አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተፈጠሩ መልካም አጋጣሚዎች ምክንያት አገሪቱ የኢንቨስተሮች መነኻሪያ እየሆነች ትገኛለች፡፡ አገሪቱ ግብርና መር የሆነውን ኢኮኖሚዋን በኢንዱስትሪ በመተካት መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገውን ጉዞ ለማሳካት ደግሞ ከዚህ ዘርፍ በሚገባ ለመጠቀም አቅዳ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በኢንቨስትመንት ዘርፉ ውስጥ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ እንደ መንገድ፣ መብራት፣ ውሃና ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮችን በበቂ ሁኔታ ማሟላት እንዲሁም የኢንቨስትመንት ድጋፎ ችንና ማበረታቻዎችንም ማቅረብ ደግሞ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ዓብይ ሚና ይጫወታሉ፡፡

ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ በአገራት መካከል የሚደረገው ፉክክር እጅግ ከባድ ነው፡፡ በከፋ የድህነት አዘቅት ውስጥ የሚገኙት ከሰሃራ በታች ያሉት የአፍሪካ አገራት እንኳ በዚሁ እሽቅድድም ውስጥ ይገኛሉ፡፡

የዓለም ባንክ የ2016 የኢኮኖሚ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በኢትዮጵያ የተመዘገበው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እ..አ በ2005 ከነበረው 265 ሚሊዮን ዶላር በ2015 በአስር እጥፍ አድጎ 2.16 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ በ2008 .ም የበጀት ዓመት ደግሞ ይህ አሃዝ ሦስት ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ያሳያል፡፡ በዚህም የምስራቅ አፍሪካን ኢኮኖሚ በበላይነት ትመራው የነበረችውን ኬንያን በመብለጥ የክፍለ አህጉሩ የኢኮኖሚ ቁንጮ ለመሆን በቅታለች፡፡

የአገሪቱን የኢንቨስትመንት እንቅስቀሴዎች በተደራጀ ተቋማዊ አሰራር ለመምራትና ለመቆጣጠር ዘርፉን የሚመራ ህጋዊ/መንግሥታዊ አካል በኮሚሽን ደረጃ ከማደራጀት ጀምሮ ትልልቅ ኩባንያዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ውጤታማ እስከማድረግ የደረሱ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

የኢ...ሪ መንግሥት ከውጭ አገራት የሚመጡ ኢንቨስተሮችን በማበረታታት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግም የተለያዩ ተግባራን አከናውኗል፡፡ ለአብነት ያህልም፣ ሌሎች አገራት የሚጠቀሙበትና ለትልልቅ ኢንቨስተሮች ድጋፍ የሚሰጥ ባለሙያ ያለበት የግንኙነት ግንባታ የሚባል ቡድን (Relationship Building Team) በማቋቋም ድጋፎችን አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ግብዓቶችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ፣ የብድር አቅርቦት እንዲመቻችላ ቸው እና ቪዛ ሳይጉላሉ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ በመሆን ስኬታማ ጉዞ ላይ የምትገኘው የምስራቅ አፍሪካዋ ኢትዮጵያ፣ ግዙፍ መዋዕለ ንዋይ የሚያንቀሳቅሱ የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብና ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የስራ እድል በመፍጠር በዘርፉ የአፍሪካ መሪ ለመሆን እየተንደረደረች እንደምትገኝ ኧርነስት ኤንድ ያንግ የተባለው ተቋም ከጥቂት ዓመታት በፊት ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል፤ የተቋሙ መረጃ ትንቢት ሆኖ አልቀረም፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር ሆናለች፡፡

በውጤታማ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ሪፎርም እና የኢንቨስትመንት አቅም ትውውቅ ‹‹የ2017 ስታር ሪፎርመር ሽልማት ››ን ከዓለም ባንክ ተቀብላለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሀገሪቱ የኢንቨስትመንት አቅሟን ለባለሀብቶች በማስተዋወቅና ፕሮጀክቶችን በማስፈፀም ረገድ ባከናወነችው ስኬታማ ተግባር ‹‹የ2017 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንቨስትመንት ሽልማት ››ን አግኝታለች፡፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንቨስት መንት ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተካ ገብረኢየሱስ ኢትዮጵያ ይህን ስኬት እንድታስመዘግብ ግብዓት የሆኗት ምክንያቶች እንዳሉ ይገልፃሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ መንግሥት ለኢንቨስትመንት ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ሰፊ እና ለዘርፉ ማደግ ያሳየው ቁርጠኝነት ጠንካራ መሆኑ በቀዳሚ ምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡

መንግሥት ኢንቨስትመንት ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ በዋጋ የማይተካ መሆኑን በማመን ለዘርፉ ማደግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

የሀገሪቱ የኢንቨስትመንት አቅም ለውጭ ባለሀብቶች የሚተዋወቅበት ዘዴ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት፣ የመሰረተ ልማትና ከአካባቢ ጥበቃና ልማት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን ችግሮች በመፍታት እንዲሁም ሌሎች የባለሀብቶችን ፍሰት ሊያሳድጉ በሚችሉ መንገዶች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በተለይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባታቸው ባለሀብቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በቀጥታ ወደ ስራ እንዲገቡ እድል ስለሚፈጥር ባለሀብቶችን ለመሳብ ትልቅ አቅም ይሆናል፡፡

እንደ አቶ ተካ ገለፃ፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መኖሩም የባለሀብቶች ፍሰት እንዲጨምር ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ይህ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በዋናው መስሪያ ቤት እና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተዘርግቷል፡፡ ይህም ባለሀብቶቹ ወደ ሌሎች ብዙ ቦታዎች መሄድ ሳይጠበቅባቸው የኢንቨስትመንት ስራቸውን ለማከናወን የሚያስፈልጓቸውን አገልግሎቶች በአንድ ቦታ ላይ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ የአሰራር ስርዓቱ የሀብት ብክነትን በማስወገድ መንግሥትንም ሆነ ኢንቨስተሮችን ተጠቃሚ የሚደርግ ተመራጭና ዘመናዊ ዘዴ ነው፡፡ በመሆኑም ከንግድ ሚኒስቴር፣ ከሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ እንዲሁም ከሌሎች መስሪያ ቤቶች በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው ማግኘት የሚጠበቅባቸውን አገልግሎቶች አንድ ቦታ ላይ በመክፈት አገልግሎቶቹን በሙሉ እንዲያገኙ መደረጉ አበረታች ለውጦችና ስኬቶች እንደሚመዘገቡ አድርጓል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስፋፋትም ባለሀብቶች ስራቸውን በጥራት ለማከናወን የሚያስፈልጋ ቸውን የሰለጠነ/የተማረ የሰው ኃይል በብዛት እንዲያገኙ ስለሚያስችላቸው ለሀገሪቱ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ማደግ የራሱን አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሕዝቡ መልካምነትና እንግዳ ተቀባይነት፣ የሀገሪቱ ሰላም እንዲሁም አምራች የሰው ኃይል መኖሩ በአፍሪካ ከፍተኛ የሆነውን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለማስመዝገብ እንዳስቻሉ ያስረዳሉ፡፡

በማስተማር እንዲሁም በጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙት ዶክተር ቆስተንጢኖስ በርኸ፣ ውጤታማ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸው ሀገራት የንግድና የኢንቨስትመንት ስራዎችን ለማከናወን ምቹ ሁኔታዎች ያሏቸው እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዘርፍ እያስመዘገበችው ያለው ስኬት ከብዙ ምክንያች ይመነጫል፡፡ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት፣ አምራች የሰው ኃይል፣ ሰፊ መሬትና ሸማች ኅብረተሰብ መኖሩ የውጭ ባለሀብቶች በብዛት ወደኢትዮጵያ እንዲመጡ ምክንያት ሆኗል፡፡ ፖሊሲውም ቢሆን የሚያሰራ በመሆኑ ለዘርፉ እድገት አወንታዊ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

እንደ አቶ ተካ ገለፃ፣ በአሁኑ ወቅት የኢንቨስት መንት ፍሰቱ እየጨመረ ነው፡፡ ወደ ሀገሪቱ በመምጣት ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እያሳዩና ቅድመ ሁኔታዎችን እያሟሉ የሚገኙት ትልልቅ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች በሌሎች የዓለም ሀገራት በሰፋፊ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ተሰማርተው ውጤታማ የሆኑና የረጅም ዓመታት ልምድ ያላቸው ድርጅቶች ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ባለሀብቶች ፈቃድ እየወሰዱባቸው ከሚገኙት ዘርፎች መካከልም ጨርቃ ጨርቅና የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡

የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች መሻሻላቸው፣ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ መሆናቸውና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በሰፊው እየተከናወነ መሆኑ ኢትዮጵያ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የምታገኘውን ጥቅም ዘላቂ ለማድረግ እንደሚያስችላት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ይናገራሉ፡፡

አቶ ተካ እንደሚሉት፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስት መንት ዘርፍ የተመዘገበውን ስኬት ቀጣይና አስተማማኝ ለማድረግም በዘርፉ አቅምና ልምድ ያላቸውን ኩባንያዎችን በመለየት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ የዘርፉን አቅም የማስተዋወቅና ስራውን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችን የማሟላት (የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ሌሎች ግብዓቶችን ማቅረብ) ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ ኩባንያዎቹን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ኢንቨስት እንዲያደርጉ የማስተዋወቅ ስራው በተለያዩ ሀገራት ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ጋር በትብብር እየተሰራ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባታቸው የኢንቨስትመንት ስራዎችን ስለሚያፋጥኑና ውጤታማ ስለሚያደርጉ የእነዚህን ፓርኮች ግንባታ አጠናክሮ ለማስቀጠል እቅድ ተይዟል፡፡ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋናው መስሪያ ቤት እና በኢንዱስትሪ ፓርኮች የተቋቋሙት የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጣቢያዎች ስራቸውን አሻሽለው እንዲሰሩ በማድረግ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት የመስጠት ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ ሰፋ ያሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ያልተደረጉባቸውን ዘርፎች በመለየት በመረጃ የተደገፉ ስራዎችን ለማከናወንም ታቅዷል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ሀገራት ትልቅ የኢኮኖሚ እድገት አቅም እያገኙ ያለው ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንደሆነና የአስተዳደርና የፖሊሲ ጉዳዮች ከኢንቨስት መንት ዘርፍ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳላቸው የሚገልፁት ምሁሩ፣ ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረዶች የበዙባቸውና በሚገባ ያልተጠኑ ፖሊሲዎች ያሏቸው ሀገራት የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ እንደሚቸገሩም ይገልፃሉ፡፡

‹‹ለወትሮው በኢኮኖሚ አቅማቸው ጠንካራ የነበሩትና የኢንቨስትመንት መዳረሻ የነበሩት የአፍሪካ ሀገራት የቀድሞ ቁመናቸውና አቅማቸው ርቋቸዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የአስተዳደር ብልሹነት፣ በናይጀሪያ ቦኮ ሃራም የሚፈፅማቸው ጥቃቶች እንዲሁም በግብፅ ደግሞ የአረብ አብዮትን ተከትሎ የተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ ትልልቅ ኢንቨስተሮች ከነዚህ ሀገራት እንዲርቁ ምክንያት ሆነዋል›› ይላሉ፡፡

ስለሆነም ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመ ንትን በመሳብ ረገድ ያስመዘገበችውን ስኬት አስተማማኝና ቀጣይ ለማድረግ መስራት ከሚጠበቁባት ስራዎች መካከል፤ የገንዘብ ተቋማት አቅምን ማጠናከር፣ ለኢንቨስትመንት የገንዘብ ምንጭ የሚሆኑ አማራጮችን ማስፋት፣ የመልካም አስተዳደርና ቢሮክራሲያዊ ጉዳዮችን ማሻሻልና የውጭ ምንዛሬ ክምችትን ማሳደግ ዋናዎቹ እንደሆኑ ይገልፃሉ፡፡

የሰራተኛ አስተዳደርና ቁጥጥርም ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነም ይመክራሉ፡፡ የሰራተኛው መብትና ጥቅም የሚጠበቅበት አሰራር ሊዘረጋ እንደሚገባ ጭምር፡፡

 

አንተነህ ቸሬ

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና ኪም ጆንግ-ኡን፤

 

ሰሜን ኮሪያ አዲስ አህጉር አቋራጭ የባሊስቲክ ሚሳይል ሙከራ ማድረጓን ተከትሎ ከልዕለ ኃያላኗ አሜሪካ ጋር የገባችበት ውዝግብ እንደገና ማገርሸቱ እየተዘገበ ነው፡፡ ሰሜን ኮሪያ አሁን የሞከረችው ሚሳይል ሁሉንም የአሜሪካ ግዛቶች መድረስ እንደሚችልም የሀገሪቱ ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡ 2017 ከገባ ወዲህ ሦስተኛው የሰሜን ኮሪያ አህጉር አቋራጭ ሙከራ የሆነው አዲሱ ሚሳይል ሀዋሶንግ 15 የሚባል ሲሆን፤ እስከ 4475 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ መምዘግዘግ እንደሚችል ተነግሯል፡፡ ይህ ደግሞ ከዓለም አቀፉ የህዋ ጣቢያ ከፍታ በአስር እጥፍ የሚልቅ ነው፡፡

የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ይፋ ያደረጓቸው ምስሎች እንደሚያመለክቱት፣ አዲስ የተሞከረው ሚሳይል ባለፈው ሐምሌ ወር በጃፓን ሰማይ ላይ ከተወነጨፈው ህዋሶንግ 14 ሚሳይል የበለጠ መጠን ያለውና ከዚህ ቀደም ከተሞከሩት የበለጠ ስፋት ያለው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሚሳይል ሙከራው በሀገሪቱ መሪ ኪን ጆንግ-ኡን አዛዥነት እንደተፈፀመ መገናኛ ብዙኃኑ ገልፀዋል፡፡ ሙከራው እንዲደረግ የሚያዝዘውን የሰውየውን ፊርማ ደጋግመው ያሳዩት የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን፣ የሚሳይል ሙከራው በኪም ጆንግ-ኡን ትዕዛዝ መሰረት በሰዓቱ እንደተፈፀመም ይፋ አድርገዋል፡፡

የሀገሪቱ መንግሥት ባወጣው መግለጫ፣ አዲስ የተሞከረው አህጉር አቋራጭ ሚሳይል በቴክኖሎጂ አቅሙ ከባለፉት ሙከራዎች የተሻለ በመሆኑ ለሀገሪቱ ጦር ጥንካሬ ልዩ ጥቅም እንዳለው አስታውቋል፡፡

የወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች እንደገለፁት ከሆነ፣ ሰሜን ኮሪያ ያስወነጨፈችው አዲሱ አህጉር አቋራጭ ሚሳይል እስከ 13ሺ ኪሎ ሜትር መጓዝ ይችላል፡፡ ይህ ርቀት ደግሞ ሰሜን ኮሪያ ባላንጣዋን አሜሪካን በዚሁ መሳሪያ ለመምታት እንደሚያስችላት ተነግሯል፡፡

አሜሪካውያን የወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች በበኩላቸው፣ ሚሳይሉ ሁሉንም የአሜሪካ ግዛቶች የማካለል አቅም ቢኖረውም ኑክሌር የመሸከም አቅሙ ግን አጠራጣሪ ነው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ አዲሱ ሙከራ በቴክኖሎጂ ከእስካሁኖቹ የተሻሻለና ለዓለም ሰላም ስጋት በመፍጠር ረገድም የከፋ እንደሆነ ባለሙያዎቹ አምነዋል፡፡

የጀምስ ማርቲን ጥናት ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ደቪድ ሽሜርለር፣ ‹‹ሰሜን ኮሪያ ያስወነጨፈችው አዲሱ ሚሳይል መላውን የአሜሪካ ግዛቶች ዒላማ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላት የሚያሳይ ነው፤ በዚህም ትልቅ ሊባል የሚችል ተግባር ማከናወን የፈለጉ ይመስላል›› ብለዋል፡፡ አዲሱ ሙከራ ከእስካሁኖቹ በተለየ መልኩ የተሻለ አቅም ሳይኖረው እንደማይቀር ገልጸው ጉዳዩን እጅግ በጥንቃቄ ማጤን እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ሙከራው ሰሜን ኮሪያውያን የጦር መሳሪያ የማበልፀግ ሀገራዊ የቴክኖሎጂ አቅማቸውን ለሌላው ዓለም ሊያሳዩ የፈለጉበት እንደሆነም ሽሜርለር አስረድተዋል፡፡

የዚሁ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ማይክል ዱትስማን በበኩላቸው፣ በሰሜን ኮሪያ የተሞከረው ሚሳይል ግዙፍ እንደሆነና ብዙዎቹ የዓለም ሀገራት ይህ ዓይነት ሚሳይል መገንባትና ማስወንጨፍ እንደማይችሉ ገልፀዋል፡፡

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምላሽ

ሰሜን ኮሪያ አዲሱን አህጉር አቋራጭ ሚሳይል ማስወንጨፏን ተከትሎ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተለመደው ውግዘት ገጥሟታል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ ውይይት አድርጓል፡፡ በውይይቱ ላይ በድርጅቱ የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሃሌይ፣ ‹‹ሰሜን ኮሪያ አዲስ የሞከረችው የባሊስቲክ ሚሳይል ሙከራ ወደ ጦርነት አፋፍ እያቀረበን ነው፤ ጦርነቱ ደግሞ የሰሜን ኮሪያን መንግሥት እስከወዲያኛው የሚያሰናብት የጠብ አጫሪነት ድርጊት ነው›› ብለዋል፡፡

የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የሰሜን ኮሪያ መንግሥትን በተደጋጋሚ ማስጠንቀቁን አውስተው፣ ሰሜን ኮሪያ እየተጓዘችበት ያለው መንገድ የዓለምን ሰላም የሚያናጋ በመሆኑ አሜሪካ የዓለምን ሰላም ለማስጠበቅ አማራጭ ለመውሰድ እንደምትገደድ አምባሳደሯ ተናግረዋል፡፡ ሁሉም ሀገራት ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የሰሜን ኮሪያን ድርጊት ፈጥነው አውግዘዋል፡፡ በሰሜን ኮሪያ ላይ አዳዲስ ማዕቀቦችን ለመጣል እንደተዘጋጁም ይፋ አድርገዋል፡፡ ፕሬዚደንቱ በትዊተር አድራሻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ከቻይናው አቻቸው ሺ ዢን ፒንግ ፋር መወያየታቸውን ገልፀዋል፡፡ ‹‹ከመከላከያ ሚኒስትር ጀምስ ማቲስና ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገናል፤ ጉዳዩ ከእጃችን የሚወጣ አይደለም›› ብለዋል፡፡

በሁለቱ መሪዎች መካከል የተደረገውን የስልክ ውይይት አስመልክቶ ከዋይት ሐውስ የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣ ፕሬዚደንት ትራምፕ አሜሪካና አጋሮቿ ከሰሜን ኮሪያ የሚሰነዘርባቸውን ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት ለመከላከል ቁርጠኛ እንደሆኑና ሰሜን ኮሪያ ከጠብ አጫሪ ድርጊቷ እንድትታቀብ ቻይና ኃላፊነቷን መወጣት እንደሚገባት ለፕሬዚደንት ሺ ዢን ፒንግ ነግረዋቸዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሬክስ ቲለርሰን በበኩላቸው፣ አሜሪካ የዓለም ስጋት የሆነችው ሰሜን ኮሪያ ከድርጊቷ እንድትታቀብ የሚያስችሉ ተጨማሪ እርምጃዎችን እንደምትወስድ ገልፀዋል፡፡

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ የሰሜን ኮሪያን ድርጊት እንደሚቃወም አስታውቆ፣ ቻይና ጉዳዩን በትኩረት እየተከታተለችው መሆኑን በቃል አቀባዩ በኩል ገልጿል፡፡ ቃል አቀባዩ ጄንግ ሹዋንግ ለጋዜጠኞች እንዳሉት፣ ሁሉም አካላት በተረጋጋ መንፈስ መንቀሳቀስ እንደሚገባቸውና ለአካባቢው ብሎም ለዓለም ሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ወታደራዊ እርምጃ መፍትሄ እንደማይሆን የመንግሥታቸውን የፀና አቋም በድጋሜ ገልፀዋል፡፡

የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ሰሜን ኮሪያን አደብ በማስገዛትና የጃፓንንና የዜጎቿን ህልውና ለማስጠበቅ መንግሥታቸው ከፍተኛውን ጥረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ከዋነኛ አጋሮቻቸው ከአሜሪካና ከደቡብ ኮሪያ ጋር በመተባበርም የቀጠናውንና የዓለምን ሰላም ለማስጠበቅ አማራጮችን እንደሚጠቀሙም ገልፀዋል፡፡

የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚደንት ሙን ጄ-ኢን በበኩላቸው፣ ከጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ጋር መወያየታቸውን ገልፀው፣ ሰሜን ኮሪያ ከድርጊቷ እንደትታቀብ የሚያስችሉ ተጨማሪ ማዕቀቦች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲጣሉባት ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ ሰሜን ኮሪያ እንደ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ባሉ ሀገራት ላይ የደቀነችው አደጋ ችላ ሊባል እንደማይገባውና ከዚህ ድርጊቷ እንደትታቀብ ለማድረግ በጋራ ለመስራት መነጋገራቸውን ከፕሬዚደንቱ ቢሮ የወጣ መግለጫ አመልክቷል፡፡

ማዕቀብ እንደ መፍትሄ?

የሰሜን ኮሪያ ጉዳይ ማዕቀብ በማብዛት መፍትሄ የሚያገኝ ቢሆን ኖሮ እስካሁን አልቆ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ አሜሪካ በተናጠል በሰሜን ኮሪያ ላይ ያዘነቡባት ተደጋጋሚ ማዕቀቦች ሀገሪቱ የሚሳይል ሙከራዋን በላይ በላዩ ከማድረግ አላገዷትም፡፡

በርካታ አካላትም በሰሜን ኮሪያ ላይ ማዕቀብ መጣል አዋጭ መፍትሄ እንዳልሆነ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት፣ የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት ሀገራቸው ሙሉ የኑክሌር መሳሪያ ባለቤት እስከምትሆን ድረስ ለማዕቀብም ሆነ ለድርድር ቦታ የላቸውም፡፡ ማዕቀብን እንደመፍትሄ አማራጭ የማይቆጥሩት እነዚህ ወገኖች ሀገሪቱ ሙሉ የኑክሌር መሳሪያ ባለቤት ከሆነች በኋላ ግን ከኃያላኑ ጋር ለመደራደር ፍላጎት ይኖራቸዋል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

በስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ጥናት ማዕከል የጥናትና ምርምር ባለሙያ የሆኑት ጣሪቅ ናኡፍ ‹‹ማዕቀብ መፍትሄነት ከሽፏል፤ ማዕቀብ የጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያ ግንባታን ለማስቆም እንደ መፍትሄ ሲሆን የታየበት የታሪክ አጋጣሚ የለም›› ብለዋል፡፡

አሜሪካና አጋሮቿ ግን አሁንም ድረስ ሰሜን ኮሪያን በማዕቀብ በማሽመድመድ ከድርጊቷ እንድትታቀብ ለማድረግ ማዕቀብን እንደአማራጭ ይዘውት ቀጥለዋል፡፡ ሰሜን ኮሪያም ማዕቀብ በተጣለባት ቁጥር ባላንጣዎቿን እያስፈራራችና የሚሳይል ሙከራውንም በላይ በላዩ እያከታተለችው ትገኛለች፡፡

ሰሜን ኮሪያና የኑክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራ

ሰሜን ኮሪያ እ..አ ከ1984 ጀምሮ ከ150 በላይ የሚሳይልና የኑክሌር ሙከራዎችን አድርጋለች፡፡ ከነዚህ መካከል ግማሽ ያህሉ ሙከራዎች የተካሄዱት የአሁኑ የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ-ኡን እ..አ በ2011 ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ነው፡፡ ሰሜን ኮሪያ የምታደርጋቸው የሚሳይል ሙከራዎች የቴክኖሎጂ አቅማቸውና የዒላማ ብቃታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ ይህም ሰፊ የሆነ የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት ካላቸው ከልዕለ ኃያላኗ አሜሪካ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ጥቃት ከተሰነዘረባት አፀፋውን ለመመለስ ሰከንዶች እንኳ እንደማታባክን ደጋግማ ገልፃለች፡፡

..አ ከ1950 እስከ 1953 ተካሂዶ የሺዎችን ህይወት የቀጠፈው የኮሪያ ልሳነ ምድር ጦርነት፣ በሰላም ስምምነት ሳይሆን ለ64 ዓመታት ያህል በቋፍ ላይ ባለ የተኩስ አቁም ስምምነት ‹‹መጠናቀቁ›› ይታወሳል፡፡ የሰሜን ኮርያ የሚሳይል ሙከራም ሆነ የኑክሌር መሳሪያ ግንባታም አሜሪካንና ደቡብ ኮርያን ብሎም ጃፓንን እንዳሳሰባቸው ይኸው በርካታ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡

(የመረጃው ምንጮች ፡ ሲ.ኤን.ኤን፣ ዘ ጋርዲያን፣ አልጀዚራ እና ቢ..ሲ ናቸው)

 

አንተነህ ቸሬ

 

Published in ዓለም አቀፍ

 

የህወሓት/ ኢህአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ ለላፉት 35 ቀናት ባካሄደው ስብሰባ የድርጅቱ ስትራቴጂካዊ አመራር ክልላዊና ሃገራዊ ተልእኮውን ከመወጣት አንፃር ያለበት ቁመና ለማየት የሚያስችል ስር ነቀል ግምገማ አካሂዷል፡፡ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ከመገንባት፤ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ መዋቅራዊ ለውጥ ከማረጋገጥ፣ የህዝባችንን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከመመለስ አንፃር ያሉበት መሠረታዊ ክፍተቶችንና አዲስቷን ፌዴራላዊት ዴሞክሰራሲያዊት ኢትዮጵያ ከመገንባት አኳያ የተጋረጡ አሳሳቢ አዝማሚያዎች በጥልቀት ገምግሟል፡፡

ይህን መሰረት አድርጎ ባደረገው ሂስና ግለሂስ ተከትሎ የእርምት እርምጃ በመውሰድና የአመራር ሽግሽግ በማድረግ ተጠናቋል፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ ህወሓት የትጥቅ ትግል ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በየደረሰበት የትግል ምእራፍ ውስጥ ሁሉ የሚገጥሙትን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች በስከነ ሳይነሳዊ ኣመራርና በኣባላቱና በህዝብ የተማላ ተሳትፎ በአስተማማኝ እየመከተ ለድል የበቃ ድርጅት ነው፡፡

የህዝብን ፀረ-ጭቆና፣ ፀረ ኃላቀርነትና ፀረ-ድህነት ትግል ለስኬት ለማብቃት የሚያስችሉ የጠራ መስመር፣ መስመሩን ለማስፈፀም የሚያስችሉ ስትራተጂዎችና ስልቶችን እየቀየሰ ከኣንድ የትግል ምዕራፍ ወደ ሌላው የትግል ምዕራፍ ለመሸጋገር የቻለበት ምስጢር ግልፅ ነው፡፡

ህዝባዊ ወገንተኝነቱ አስተማማኝ የሆነ፣ ፈተናዎች በገጠሙት ቁጥር ራሱን በሚገባ እየፈተሸና ወቅቱ የሚጠብቀውን ፤ ማንኛውንም የእርምት እርምጃ እየወሰደ ጥንካሬዎቹን የሚያጎለብት ድክመቶቹ ያለምህረት በማስወገድ በመስዋእትነት የደመቀ ታሪክ መስራት የቻለ ኣመራር ባለቤት በመሆኑ ነው፡፡

ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ከእህትና አጋር ድርጅቶችና ከመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን በከፈሉት እጅግ ከባድ መስዋእትነት አዲሱቷን ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ችለዋል፡፡ በአገራችን ታሪክ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የልማትና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና የህዳሴ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡

ይሁንና በትጥቅ ትግልም ወቅት ሆነ በልማትና በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንቅስቃሴያዎችን እጅግ የሚያኮራ ተግባራትን የፈፀመ ድርጅት ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ከችግር ኣዙሪት መውጣት አቅቶት የሚንገዳገዱበትና ለህዝብ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ መስጠት ላይ ሰፊ ድክመት እያሳየ የመጣበት ሁኔታ ተፈጥረዋል፡፡

በተለይም ካለፉት ጥቂት ኣመታት ወዲህ ስትራቴጂካዊ ኣመራሩ እየተዳከመ ተልእኮውን ለመወጣት የሚያስችል ቁመና፣ ኣመለካከትና ኣደረጃጀቱ በየጊዜው እየተሸረሸረ፣ ህዝባዊነቱ እየቀነሰ፣ የህዝብን ችግር በማያወለዳ መልኩ ሳይፈታ በትንንሽ ድሎች የሚረካ ሆኖ በመገኘቱ ምክንያት የመፍትሔ አካል ከመሆን ይልቅ የችግር ምንጭ መሆን የጀመረበት ሁኔታ በስፋት መታየት ከጀመረ ውሎ ኣድራል፡፡ ይህንን ቁመና ይዞ መስመሩንና የመለስን ለጋሲ ማስቀጠል የሚቻልበት ሁኔታ እንደሌለ በግልፅ አይቷል፡፡

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ማእከላዊ ኮሚቴው ከገባባት ኣዙሪት ለመውጣት ያለው ብቸኛ አማራጭ በድርጅት የቆየ ሳይነሳዊ የትግል ባህልና ታሪክ መሰረት በቁጭት ተነሳስቶ ጥልቀት ያለው የአመራር ግምገማ ማድረግ ብቻ እንደሆነ በማመን በኣፅንኦት መክራል፡፡

ያጋጠሙትን ፈተናዎች በጥሞና መርምሮ ድርጅቱን በማያዳግም ሁኔታ ወደ ትክክለኛው መስመሩና ህዝባዊ ወገንተኝነቱ ለመመለስ በሚያስችለው መልኩ ራሱን በጥልቀት ፈትሿል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ስደረጉ ከነበሩት የይስሙላ ግምገማዎች በዓይነቱና መልኩ በተለየ ችግሮቹን በሚገባ ለመለየት ያስቻሉት መተጋገል አካሂዷል፡፡

ወደ ግምገማ ሲገባ አሁን በስራ ላይ ያለውና ተተኪው አመራር በጋራ ትኩረት ሰጥቶ ያየው ጉዳይ ከገባበት የአመራር አዙሪት ውስጥ ለመውጣት በተለመደው መንገድ መሄድ በፍፁም የማይዋጣ መሆኑን በመገንዘብ ከተለመደው ግምገማ ለመውጣት ያስችላል ተብሎ የታመነበትና ስፋትና ጥልቀት ያለው ክርክር የጋበዘ የድርጅቱን ኣጠቃላይ ሁኔታና የኣመራሩን ድክመት በሚገባ የፈተሻ ሰነድ ለኣመራሩ ቀርቦ ሰፊ ውይይትና ክርክር ተደርጎበታል፡፡

በዚህ መድረክ በቀረበዉ ሰነድ ላይ ተመስርቶ በተደረገ ጥልቅ ዉይይት የህዝባችንና የመላው አባላችንን ተደጋጋሚ ጥያቄ ለመመለስ ያልተቻለው በዋናነት ስትራቴጂክ አመራሩ ከገባበት አዙሪት ውስጥ መውጣት አቅቶት ሲዳክር በመቆየቱ መሆኑን የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ አረጋግጧል፡፡

አመራሩ የሃሳብና የተግባር አንድነት የጎደለው፣ ፀረ ዴሞክራቴክ ተግባርና አስተሳሰብ ውስጥ በስፋት የተነከረ፣ በተልዕኮ ዙርያ በመተጋገልና በመርህ ላይ የተመሰረተ አመራር የማይሰጥ፣ ህዝብንና አላማን ከማስቀደም ይልቅ የራሱን ክብርንና ጥቅም የሚያስቀድም መሆኑ ታይቷል፡፡

ለህዝብ ያለው ወገንተኝነት እየተሸረሸረ፣ ከኣገልጋይነት ይልቅ ራሱን እንደ ተገልጋይ እየቆጠረ፤ መዋቅራዊ ለውጥ በሚያመጡ ስኬታማ የህዝብ ዙርያ መለስ እንቅስቃሴ ከመጠመድ ይልቅ በተደማሪ ለውጦች የሚረካና በውሸት ሪፖርት ራሱን መሸለም የሚቃጣው አመራር እየሆነ በአጠቃላይ ራሱን ወደ ጥገኛ ገዢ መደብ የመሸጋገር አዝማሚያ የተጠናወተው መሆኑን በትክክል አስፈቀምጧል፡፡ ይህ የስትራተጂካዊ አመራር ድክመት በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግቦቻችን አፈፃፀም ላይ እጅግ ከባድ ተፅእኖዎች ፈጥረዋል፡፡

በህዝብ ዙርያ መለስ ተሳትፎና በጠራ መስመር ማስመዝገብ የጀመርናቸውን በርካታ ለውጦች ማስቀጠል ያልተቻለበት አንዳንዴም ወደሃላ መመለስ የጀመሩበት ሁኔታ እንደነበረ በጥልቀት ታይታል፡፡ ሁሉንም የልማት ሃይሎች በተደራጀ መልኩ በመምራት ረገድ የነበረውን ሰፊ ክፍተትንም ኣይቷል፡፡

ወጣቶች ፣ ምሁራን፣ ሴቶችና ሌሎችም የሞያ የማሕበራትና መሰል ኣደረጃጀቶች የለውጥ ባለቤት ሆነው የሚውጡበትን ዕድል በማምከን ድርጅቱን በቀጣይነት የሚመራ ብቁ ሃይል እንዳይፈጠር እንቅፋት የሆነ ኣመራር መሆኑንም በሚገባ ተረድቷል፡፡ ህዝቡ በድርጅቱ ላይ የነበረዉን እምነት እንዲሸረሸርም ትልቅ አስተዋፅኦ ኣድርጓል፡፡

በአመራሩ ዘንድ የታየው ድክመት በህዝብ ዘንድ ካስከተለው ከፍተኛ የአመኔታ መሸርሸር ችግር በተጨማሪ በከተማም በገጠርም በጀመርናቸው ትራንስፎርሜሽንና ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥ ሰራዎቻችን ለአደጋ ያጋለጠ እንደነበረ ማእከላዊ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡

በገጠርም በከተማም የቀረፅናቸው ፖሊስዎችና የቀየስናቸው ስትራተጅዎች ትክክለኝነት ላይ የሚያጠራጥር ነገር ባይኖርም ኣፈፃፀማችን የደረሰበት ደረጃ ባቀድነው ልክ ኣስተማማኝ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ በህዝባችን ዘንድ ተገቢ ጥርጣሬ እንዲያድርበት ማድረጉም በትክክል ለይቷል፡፡

በገጠር የእርሻ ትራንስፎርሜሽን፣ በከተማ የኣነስተኛና ጥቃቅን ልማት፣ የከተሞች እድገት፣ የወጣቶች እና ሴቶች ስራ ፈጠራ እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዕድገት ባቀድነዉ ልክ ላለመመዝገቡ የስትራተጂክ አመራሩ ድክመት ዋናውን ድርሻ እንደሚወስድ ገምግሟል፡፡

የችግሩን ጥልቀትና የኣመራሩን ሁኔታ በስፋት ከገመገመ በኃላ ማእከላይ ኮሚቴው ለተፈጠረው የአመራር ችግር ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት በማመን ቀጥሎ ያከናወነው በመላው የማእከላይ ኮሚቴው ኣባላት የሚደረግ የሰላ ሂስና ግለሂስ ነው፡፡

ለተፈጠረው ችግር ማእከላዊ ኮሚቴው በኣጠቃላይ ተጠያቂ ቢሆንም የችግሩ የከፋ መገለጫ የህወሓት ስራ ኣስፈፃሚ ኮሚቴ እንደ ኣካልም ሆነ እንደ ግለሰብ ኣመራሩ መሆኑን በመውሰድ ጥልቅ የሂስና ግለ ሂስ መድረክ ኣካናውኗል፡፡

የሂስና ግለሂስ መድረኩ አላማ በግለሰብ ኣመራር አባላት ላይ ያተኮረ ሳይሆን ድርጅቱ ካለዉ ስትራተጂካዊ ፖለቲካዊ ተልእኮ አንፃር እያንዳንዱ አመራር ሃላፊነቱን የተወጣበትን ደረጃ እና ልክ በትክክል ለመገንዘብ እና አስፈላጊዉን የእርምት እርምጃ ለመዉሰድ ያለመ ነበር፡፡ ሂደቱም በግልፅነት ፣ በሙሉ ተሳትፎና በቁጭት መንፈስ የተከናወነ ሲሆን በመጨረሻም መላዉ አመራር ዘንድ በተደረሰበት ድምዳሜ ዙርያ የጋራ መግባባት የተያዘበት ሁኔታ ተፈጥራል፡፡

ማእከላይ ኮሚቴዉ የሂስና ግለሂስ ሂደቱን ካከናወነ በኃላ በድርጅቱ ስትራቴጂክ አመራር ዘንድ በስፋት ይስተዋል የነበረዉን የሃሳብና የተግባር አንድነት ችግር ስር ነቀል በሆነ መልኩ ለመፍታት የሚያስችል መግባባት ላይ የተደረሰበት የአመራር ሽግሽግ በማድረግ የተሃድሶው ስትራቴጂክ አመራር ተጠናክሮ የወጣበት የተመቻቸ ሁኔታ ፈጥሯል ፡፡

የተከበራችሁ የድርጅታችን አባላት፣ አርሶ አደሮችና የከተማ ነዋሪዎች

ህወሓት የትግራይ ህዝብ የትግል ውጤት እና መሪ ድርጅት ነው፡፡ጥንካረው ለህዝቡ ካለው ታማኝነትና ወገንተኝነት የሚመነጭ ነው፡፡ ህወሓት ፈተናዎች ባጋጠሙት ቁጥር ከህዝብና አባላቱ ጋር በመሆን ችግሩን እየፈታ ለበርካታ አስርት ዓመታ ዘልቋል፡፡ ባለፉት ዓመታት ጥያቄዎችህን በመፍታት ረገድ የህወሓት አመራር ከፍተኛ ድክመት አሳይቶም ጭምር በትዕግስት እና በተስፋ መጠበቃችሁ ድርጅቱ ይገነዘባል፡፡

ማእከላይ ኮሚቴው ችግሩን በሚገባ ተረድቶ የናንተን ጥያቄዎችንና ፍላጎቶች ለመፍታት፣ በህዝብ ዘንድ በብዙ መልኩ ተሸርሽሮ የነበረውን አመኔታ ለማሳደስ የሚተጋ፣ በሃገር ኣቀፍ ደረጃ ሊኖረን የሚገባውን ገንቢ ሚና ለማስቀጠል ዝግጅነቱ ፣ ተኣማኒነቱና ፅናቱ ያለው፤ ስኬቶቻችንን ለማስቀጠል የቆረጠና ቀጣዩን ጉባኤ ኣሳታፊ በሆነ መልኩ ለማከናወን የሚያስችል ስራዎችን የሚሰራ ኣመራር እንደሚሆን ኣንጠራጠርም፡፡ አመራሩ በጊዜ የለም መንፈስ ከመላው አበላችንና ህዝባችን ጋር በሚደርገው ጥልቅ ውይይት ያስቀመጣቸው ኣቅጣጫዎች በበለጠ ለማበልፀግ የሚያስችል ስራ የሚሰራ ይሆናል፡፡

የጉባኤ ዝግጅታችን መላው አባላችን፣ ምሁራን፣ ወጣቶች ፣ ሴቶችና ቡዙሃን ማሕበራትን በነፃነት ባሳተፈ መልኩ እንዲካሄድና በተመረጡ የህዝብ አጀንዳዎች ላይ አተኩሮ ለማካሄድ የሚያስችል ዙርያ መለሽ ዝግጅት የሚደረግ ይሆናል፡፡ እንደተለመደው ሁሉ አሁንም ከጎናችን ቁማቹህ ለጥቅማቹህ መረጋጥ እንድትታገሉ ድርጅታቹ ህወሓት ጥሪውን ያቀርባል ፡፡

የተከበራችሁ የክልላችን ምሁራንና ልማታዊ ባለሃብቶች

የህወሓት/ ኢህአዴግ አመራር በሚፈለገው ደረጃ የተመቻቸ ሁኔታ ባለመፈጠሩ ምክንያት በክልላችሁና በሃገራችሁ ጉዳይ ላይ በሚገባው ደረጃ ያላሳተፍናችሁ መሆኑን ተገንዝቧል በመሆኑም ጥያቄያችሁን ለመመለስ የራሳችሁን የተሟላ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ህወሓት/ኢህአዴግ ምሁሩና ባለሃብቱ በመሰላችሁ አደረጃጀት ውስጥ ሁናችሁ ተዋናይ የምትሆንበት ተቋማዊ መሰረት በማስቀመጥ ከልቡ የሚሰራ ይሆናል፡፡ በጥናትና ምርምርም ሆነ በልማት የክልላችንም ሆነ የሃገራችን ልማትና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ባለቤት የምትሆኑበት ሁኔታ ይመቻቻል ፡፡

የተከበራችሁ የክልላችን ወጣቶችና ሴቶች

በክልላችን ልማትም ሆነ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላችሁ ተሳትፎ ለሃገራችን ዕድገትና ህዳሴ መረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡ ከምንም በላይ የተጠቃሚነትና የተሳታፊነት ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚንቀሳቀስ ድርጅታችሁ ህወሓት/ኢህአዴግ ቃል ይገባል ፤ እናንተን በፅሞና ለማዳመጥና ለማታገል የሚያስችሉ መድረኮችንም ያመቻቻል ፡፡

ዉድ የኢህአዴግ እህትና አጋር ድርጅቶች

በልማትና በመልካም አስተዳደር ዙርያ ህዝባችን ለከፍተኛ ምሬት የዳረጉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በኣመራሩ ድክመት የተፈጠሩ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ድርጅታችን ህወሓት/ ኢህአዴግ በአገር ደረጃ በሚደረጉ የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎቻችን በማሳካት ረገድ ሲጫወት በመጣው ሚና ላይ ኣሉታዊ ተፅእኖ መፍጠሩንም በሚገነባ ይገነዘባል፡፡

የኣመራር ድክመት በህወሓት ውስጥም ሆነ በክልላችን በሚደረጉ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጥረቶች ላይ ጉዳት ከማድረሱ በተጨማሪ በእህትና በአጋር ድርጅቶች መካከል ለበርካታ ኣስርት ኣመታት የነበረውን በመርህ እና በትግል ላይ የተመሰረተ ውህደት፣ ለዙርያ መለሽ ስኬት ያበቃን የአመለካከትና የተግባር ኣንድነት በየጊዜው እየተሸረሸረ እንዲመጣና በጋራ ዓለማ ዙርያ በአንድ ልብና መንፈስ ከመንቀሳቀስ ይልቅ በንትርክና በጥርጣሬ መተያየት ያጠላበት እንዲሆን በማድረግ በኩል የራሱን ኣሉታዊ ኣስተዋፅኦ እንደደረገ በትክክል ኣስቀምጧል፡፡

ሁሉንም አቅሞቻችን፣ የህዝባችንን ፍትሓዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ የጠሩ ፖሊሲዎቻችን ሲኬታማ ኣፈፃፀም ላይ ከማድረግ ይልቅ የፌዴራል ስርዓት ጠላቶች ባጠመዱልን ወጥመድ ውስጥ ገብተን የሃገራችንን ኢትዮጵያ ህልውና ፈተና ላይ እንዲወድቅ በማድረግ ረገድ በህወሓት ኣመራር ዘንድ የታየው ድክመት የማይናቅ ሚና እንደነበረው በግልፅ ይረዳል፡፡

የፈዴራል ስርዓቱን ለመናድ ከውስጥም ከውጭም የተሰባሰቡ ጥገኛ ሃይሎችን በጋራ የመመከት ኣቅማችን እየተመናመነ በተመሳሳይ ፕሮግራምና ልማታዊ መስመር ዙርያ የተሰለፉ ሃይሎች የጋራ ትግላቸዉ መደነቃቀፍ የጀመረበት ሁኔታ ተፈጥራል፡፡

በኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች ውስጥ ለሚታዩ ችግሮች ዋነኛው ተጠያቂነት ለየድርጅቱ ኣመራር የሚተው ቢሆንም በህወሓት ኣመራር ውስጥ ይታዩ የነበሩ ኣዝማሚያዎች ለብዙ ኣስርተ ዓመታት በእሳት ጭምር ተፈትኖ የመጣውንና ለሃገራችን ኢትዮጵያ ልማትና ዴሞክራሲ እውን መሆን ምክንያት የሆነው አብዬታዊና ዲሞክራሲያዊ አንድነት በመሸርሸር ረገድ የማይናቅ ድርሻ እንዳነበረው ማእከላዊ ኮሚቴው ባደረገው ግምግማ ኣረጋግጧል፡፡ ህወሓት ከእህት እና አጋር ድርጅቶች ያለውን ግንኝነት በመርህና በመተጋገል ላይ በመመስረት የሚታደስበት የነበሩ የርስ በርስ መጠራጠሮች ለመፍታት የሚያስችሉ ኣቅጣጫዎችን የሚከተል ይሆናል፡፡

ዉድ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች፣ ላብአደሮች፣ ልማታዊ ባለሃብቶች

ህወሓትና የትግራይ ህዘብ ከሌሎች እህትና ኣጋር ድርጅቶች እንዲሁም ከመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን ለእኩልነትና ለፍትሓዊ ተጠቃሚነት የከፈሉት እጅግ ከፍተኛ መስዋዕትነት ሳይበቃውና ተከታታይ ገዢዎች ያሲረፉበት ቁስል በወጉ ሳያገግም ለሌላ የተቀናጀ ጥቃት የሚጋለጥበት ሁኔታ ከመፍጠር ኣንፃር የህወሓት ኣመራር ውስጥ የታየው ድክመት የማይናቅ ኣስተዋፅኦ ኣድርጓል፡፡

አሁንም ቢሆን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ያመጣቸዉን ትሩፋቶች ጠብቆ የተሻለ ብልፅግና የሰፈነባት እና ህዳሴዋ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን እዉን ለማድረግ በሚደረገዉ እንቅስቃሴ ዉስጥ ድርሻዉን ኣጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ከዉጭም ከዉስጥም የሚቃጡብንን አፍራሽ ጥቃቶች ለመመከት ከመላዉ የሃገራችን ህዝቦች ጋር በቅርበት ይሰራል፡፡ በአሁኑ ሰአት በየአካባቢዉ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትና የህዝቦች የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር እንዲሁም የልማት ጥያቄ በተገቢዉ መንገድ ለመመለስ በሚደረገዉ ርብርብ ዉስጥ ድርሻዉን ለማበርከት ዝግጁነቱን ይገልፃል፡፡

ህወሓት/ኢህኣዴግ የጋራ ሃገራችንን በሆነችው ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለልማትና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የተጫወተውን ገንቢ ሚና ኣጠናክሮ ለመወጣት የሚያስችለውን ኣቅጣጫዎች ከህዝቦች ጋር በመመካከር የሚያከናውን ይሆናል፡፡ ዲሞክራሲያዊ አንድነታችሁን አጠናክራችሁ አፍራሽ አጀንዳዎቻችውን ለማሳካት ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚዳክሩ ጠላቶችን በጋራ እንድንመክት ጥሪውን ያቀርባል ፡፡

 

የህወሓት ማ/ኮሚቴ

ክብርና ሞገስ ለትግሉ ሰማእታት

ህዳር 21/2010 .

 

 

 

 

Published in አጀንዳ

 

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በጋራ የሚያከብሩት ዓመታዊ በዓል የሕዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት እያጎለበተና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን እያሰረፀ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ የኢ.... ህገ መንግስት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ሆነው በእኩልነት ላይ በተመሰረተ አንድነት ለመኖር የገቡትን ቃል የሚያረጋግጥ የሕዝቦች ትስስር መገለጫ ዋስትና ሆኗል፡፡

ህገ መንግስቱ ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በራሳቸው ተዘጋጀቶ ለራሳቸው ጥቅም የሚውል በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ለመኖር ያስችለናል በሚል መክረው በተወካዮቻቸው አማካኝነት ያጸደቁት የማንነታቸው መገለጫ ነው።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀደም ሲል በህገ መንግስት ድንጋጌ ያላገኙትን መብት የተጎናፀፉት በዚሁ ሕገ መንግስት ነው። ፍርድ ቤት ቆመው በቋንቋቸው እንዲዳኙ፣ እንዲማሩ፣ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የበቁትም በዚሁ ሕገ መንግስት አማካይነት ነው።

ኢትዮጵያውያን ብረት አንስተው ጨቋኝ ሥርዓትን የተፋለሙት መሰረታዊ ማንነታቸውን የሚያሳጣና ሰብዓዊ ክብራቸውን የሚጋፋ አስከፊ ሥርዓት ስላጋጠማቸው ነበር፡፡ በዚህ ሂደት የህይወት መስዋዕትነት ከፍለው ሥርዓቱን ላይመለስ አስወግደውታል። ይህ የተባበረ ክንድ አንድነቱን አጠንክሮ ለልማት በመነሳት ባከናወነው ተግባር ዛሬ አገሪቱ የደረሰችበት የልማት ደረጃ ላይ ማረፍ ተችሏል።

ይህን በጋራ አብሮ የመልማት ትስስር በማጠንከር መጪውን ጊዜ የበለጠ የዕድገትና የብልፅግና ማድረግ ከሩቅ አሳቢ ዜጎች የሚጠበቅ ቢሆንም የአገሪቱን መልካም ዕድገት የማይፈልጉ የውስጥና የውጭ ባላንጣዎች የሚያከናውኑት አፍራሽ ተግባራት ለልማት እንቅፋት ስለሚሆን እኩይ ተግባራቸውን ለመመከት ነቅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡

በብዙዎች መስዋዕትነት የተገኘውን ሰላም ለማደፍረስና ለሕዝቦቿ መበጣበጥን የሚመኙት ጠላቶቿ እነርሱ በሰላም አገር ተቀምጠው ፣ልጆቻቸውን በሰላም እያስተማሩ፣ ሥራቸውን በሰላም እየሰሩ ሲሆን፤ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጩትን አገርን የማበጣበጥ ተግባር በነቃ የሕዝብ ተሳትፎ ውድቅ ማድረግ አማራጭ የሌለው ውሳኔ መሆኑን በጥሞና መገንዘብ ያሻል፡፡

ዜጎች አገሪቱን አሁን የደረሰችበት ደረጃ ለማድረስ በአካልም በገንዘብም በከፈሉት መስዋዕትነት በዓለም አቀፍ ደረጃ መጠራታችን አስከፊ የነበረው ገፅታችን መለወጡን የምናይበት በመሆኑ ልባችን ደስታን ተጎናፅፎ ፣ በቀጣይ ከዚህ በበለጠ ከፍ የምንልበትን ተግባር የምናከናውንበት እንጂ ባገኘነው ድል ተኩራርተን እጆቻችንን አጣጥፈን የምንቀመጥበት መሆን የለበትም፡፡

መጪው ጊዜ የአገራችን ስም በበለጠ መልካምነትና በዕድገት የሚጠራበት እንዲሆን ዛሬ የምናከናውነው በጎ ተግባር መሰረት ስለሚሆን ለነገ የላቀ ዕድገታችን እያንዳንዷን የዛሬ ተግባራችንን በበጎ ሁለገብ ጥረታችን ማለምለም ይኖርብናል፡፡

መቼውንም ቢሆን ማንኛውም ተግባር ሲከናወን ሁሉም ጉዞ አልጋ በአልጋ እንደማይሆን በመረዳት፤ችግሮች ሲያጋጥሙም በውይይት በመፍታት እስካሁን የተገኘውን ድል ወደተሻለ ደረጃ በማሳደግ የላቀ ከፍታ ላይ መድረስ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነው፡፡

ይህ በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በኢፌዴሪ ህገመንግስት በተጎናፀፉት መብት በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነታቸውን በማጠናከር ዓለምን ያስደመመ ዕድገትን እንዳመጡ ሁሉ ዛሬም ያንኑ አንድነታቸውን ለዓለም በማሳየት የአገሪቱን ታላቅነት የሚያረጋግጡበት ሕብረታቸውን ማስመስከር ይኖርባቸዋል፡፡

በየዓመቱ ህዳር 29 የሚከበረው የብሄሮች፣ የብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀንም የኢትዮጵያውያን የአንድነት ቀን በመሆኑ መላ የአገሪቱ ሕዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው ልማታቸውን የሚያጠናክሩበት፣ ያገኙትን ሰላም የሚያጣጥሙበትና አንድነታቸውን የሚያሳዩበት ወሳኝ ወቅት ሊሆን ይገባል፡፡

 

 

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ

 

በጌዴኦ ዞን በቅርቡ በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ የተፈናቀሉ ከ19 ሺ በላይ ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን የጌዴኦ ዞን ገለጸ፡፡ ለተፈናቃዮቹ በንግድ ስራ ይተዳደሩ የነበሩ ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም የክልሉ መንግስት 20 ሚሊዮን ብር መድቧል፡፡

በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደተናገሩት፤ በዞኑ ተቻችሎና ተከባብሮ በሚኖረው ህዝብ መካከል መስከረም 27 እና 28 ቀን 2009 .ም ጠባብነት የሚያጠቃቸው አካላት በቀሰቀሱት ሁከትና ብጥብጥ የሰው ህይወት የጠፋ ሲሆን፤ በአካባቢው በሰላም ይኖሩ የነበሩ 19800 ነዋሪዎች እንዲፈናቀሉና የ9600 ሰዎች ንብረታቸው እንዲወድም ምክንያት ሆኗል፡፡

በወቅቱ ከንብረታቸው የተፈናቀሉ ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋምና ወደነበሩበት አካባቢ ለመመለስ በተደረገው ጥረት የክልሉ መንግስት 60፣ የዞኑ 40 በመቶ ወጪዎችን በመሸፈን በሁከቱ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸው 174 ንግድና መኖሪያ ቤቶች ውስጥ 902 ቤቶች ተጠናቅቀው ነዋሪዎቹ መልሰው እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን፤ ቀሪዎቹን ለመገንባት የሰባት ቤቶች ግንባታ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

አቶ ኃይለማርያም «ከተፈናቃዮቹ ውስጥ በንግድ ይተዳደሩ ለነበሩ አካላት ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ የክልሉ መንግስት20 ሚሊዮን ብር የመደበ ሲሆን፤ ተጎጂ ነጋዴዎችን የመለየቱ ስራ ተጠናቅቆ ወደ ተግባር ለመግባት በዝግጅት ላይ ነው፡፡ ጥፋተኖችን ተጠያቂ ለማድረግ በተደረገው እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ በእኩይ ተግባሩ ተሳትፈዋል ያላቸውን 3400 ሰዎች አጋልጦ የሰጠ ሲሆን፤ የተጠረጠሩትም ሰዎች ለህግ እንዲቀርቡ ተደርጓል» ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ኃይለማርያም ገለጻ፤ በእሸትና በደረቅ ቡና ኢንዱስትሪዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ የፌዴራል መንግስት ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፤ ንብረታ ቸው ያልተጎዳባቸውን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የማድረግና አካባቢውን የማረጋጋት ስራዎችም ተሰርተዋል፡፡ የአካባቢውን ሰላም ለማደፍረስ የሚጥሩ አካላትን ለመከላከል የተቀናጀ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ የሰላም ጉዳይ በመንግስት ብቻ የሚጠበቅ ባለመሆኑ በየደረጃው ከህዝቡ ጋር ውይይትም እየተደረገ ነው፡፡ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞኑ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚገኙበት የሰላምና የልማት ኮንፈረንስ ህዳር 23 ቀን 2010 ለማካሄድ ዝግጅቱ ተጠናቅቋል፡፡

 

ዑመር እንድሪስ

Published in የሀገር ውስጥ

 

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ኢንዱስትሪው የሚፈልጋቸውን ዘሮች በማባዛት ለተጠቃሚው በማቅረብ በኩል የነበሩበትን ውስንነቶች ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር አቅርቦት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈለቀ ገዛኸኝ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለፁት ድርጅቱ ለረጅም አመታት በትኩረት ሲሰራ የቆየው በሰብል እህሎች ላይ ሲሆን፣ ከ20 በላይ ሰብሎችና ከ70 በላይ ዝርያዎች እያባዛ ለተጠቃሚው በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡ በአቅርቦት በኩልም ችግር አላጋጠመውም። በአሁኑ ጊዜ ተፈላጊ የሆነውን የመካሮኒ ስንዴ እንዲሁም የቢራ የገብስ ብቅል አትክልቶች፣ ቅመማቅመሞች እና የሰሊጥ ዘሮችን አባዝቶ በማቅረብ በኩል ውስንነቶች ነበሩበት፡፡ በመሆኑም የቢራ ገብስ ብቅል፣ለፓስታና መካሮኒ የሚሆን ስንዴ እንዲሁም የተለያዩ አትክልቶችን በማምረት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ከውጭ በማስመጣት እንደሚጠቀሙ አመልክተዋል፡፡

እንደ ሽንብራ፣ ቦሎቄ፣ ባቄላ ያሉ ጥራጥሬ፤ ከቅባት እህሎች ደግሞ ሰሊጥ፣ ተልባ፣ ለውዝ የመሳሰሉት፣ ከቅመማ ቅመምም ጥቁር አዝሙድ በውጭ ገበያ ተፈላጊነታቸው መጨመሩን የገለፁት አቶ ፈለቀ በእነዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባ ኮርፖሬሽኑ መገንዘቡን አስታውቀዋል፡፡

እንደሥራ አስፈጻሚው ማብራሪያ ኮርፖሬሽኑ እቅዱን ለመተግበርም ከኢትዮጵያ ሆርቲካልቸርና ግብርና ኢንቨስትመንት ባለስልጣን፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከአርሶ አደሩ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡

ሥራ አስፈጻሚው ከውጭ ዘር አቅራቢዎች ጋር ለመስራት ቅድመ ሁኔታዎች እያመቻቸ በመሆኑ በጥራትም ሆነ በዋጋ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ መሥራት እንደሚጠበቅ ገልፀው፤ ኮርፖሬሽኑ ግብአቶችን በአንድ መስኮት አገልግሎት ለማቅረብም በጥረት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

 

ለምለም መንግሥቱ

 

 

 

 

 

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።