Items filtered by date: Saturday, 02 December 2017

የዊልቼር ቅርጫት ኳስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተወዳጅነትን አግኝቷል፤

 

በፓራሊምፒክ ስፖርቶች ትኩረት ከሚሰጣቸው የውድድር አይነቶች አንዱ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ነው። ይህ በአገራችን ከተጀመረ አጭር ጊዜ የሆነው የዊልቼር ቅርጫት ኳስ 2006 .ም ላይ ባህርዳር በተካሄደው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ነበር በአገራችን የተዋወቀው። በወቅቱ ስፖርቱ ለአገራችን አዲስ ከመሆኑ አኳያ ለመላ ኢትዮጵያ ጨዋታ በመጡ የፓራሊምፒክ ተወዳዳሪዎች ነበር የተዋወቀው። እነዚህ ተወዳዳሪዎች ስፖርቱን ለማስተዋወቅ ያደረጉት ጥረትም ስፖርቱ ከአካል ጉዳት ጋር አስቸጋሪ ይመስል ነበር። አሁን በጣት ከሚቆጠሩ ጥቂት ዓመታት በኋላ ግን ስፖርቱ በከፍተኛ ደረጃ በአገራችን ተስፋፍቶ ተወዳዳሪዎች ከአካል ጉዳት ጋር ከባድ እንዳልሆነ የሚያስመ ሰክሩበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ከዚህም በዘለለ አገራችን በዚህ ስፖርት ጥረት ከታከለበት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉ ስፖርተኞች እንዳሏት ፍንጮች መታየት ጀምረዋል።

ስፖርቱ በአገራችን ሲጀመር በሃያ አራት ዊልቼሮች በአምስት ጣቢያዎች ብቻ እንደነበር የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ ሂደት ዳይሬክተር አቶ ይመር ኃይሌ ያስታውሳሉ። በቀጣይም ከዓለም አቀፉ የቀይመስቀል ማህበር ጋር በመተባበር የስልሳ ዊልቼሮች ድጋፍ ተገኝቶ እድሉ ላልደረሳቸው የተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ ፕሮጀክቶች ተከፋፍሏል። ከዚያም በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፖርቱ ትልቅ ደረጃ የደረሱ ባለሙያዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስመጣት የአቅም ግንባታ መሰረታዊ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርም ይህን ተመልክቶ እንደ አንድ ትምህርትና ስልጠና በሁሉም ክልሎች እንዲሰጥ አድርጓል። በዚህም አሁን ላይ ስፖርቱ አገር አቀፍ ይዘት ሊኖረው ችሏል። አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ክልል፣ ድሬዳዋና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሮች ላይ ስፖርቱ እንደተስፋፋ የሚገልፁት አቶ ይመር በቀጣይ በድጋፍ በሚገኙ ዊልቼሮች ስፖርቱ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች እንዲደርስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ስፖርቱ በክልል ደረጃ ባሉ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፊ ተቀባይነትን አግኝቶ እየተስፋፋ ቢገኝም የበለጠ ለማሳደግ ክለቦች ሊይዙት ይገባል። ለዚህ ግን በፌዴሬሽኑ በኩል አንድ ትልቅ ሥራ ይቀራል። ይህም አሁን በቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ላይ ጥገኛ ሆኖ የሚገኘውን የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ኮሚቴ ወደ ማህበር ወይንም አሶሴሽን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ የሥራ ሂደት ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ። «ኮሚቴው ወደ ማህበር ሲያድግ የራሱ ፅህፈት ቤት ይኖረዋል፤ መንግሥትም ይደግፈዋል፤ የማህበሩ አባላትም ከዓለም አቀፍ አቻ ማህበራት ጋር ግንኙነት እያደረጉ የራሱን የገቢ ምንጭ እንዲኖረው ያደርጋሉ፤ ከዚያም ወደ ክለቦች መሄድ ይቻላል» በማለትም አቶ ይመር ገልፀዋል።

ስፖርቱን የበለጠ ለማስፋፋት የቅርጫት ኳስ የክለብም ይሁን ሌሎች ውድድሮች በተለያዩ አካባቢዎች ሲካሄዱ በቅድሚያ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ውድድሮች እየተደረጉ የበለጠ ለማስተዋወቅ ጥረት ይደረጋል። ይህ ብቻ ግን በቂ እንዳልሆነና ሌሎች ሥራዎችን ለመስራት ብዙ ነገሮች እንደሚያስፈልጉ አቶ ይመር ይናገራሉ። አካል ጉዳተኞችን ከቦታ ቦታ ለማዘዋወር የራሱ የሆነ ትራንስፖርት እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች ከመኝታ ጀምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶች መሟላት እንዳለባቸውም ያስረዳሉ። መንግሥት በአካል ጉዳተኞች ላይ ትልቅ ትኩረት በማድረጉና የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማህበርም የሚደግፈው በመሆኑ እነዚህ ችግሮች በሂደት እንደሚቀረፉም አቶ ይመር እምነት አላቸው።

የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ውድድር መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ውስጥ ተካቷል። በዚህም ዘንድሮ መቀሌ በሚካሄደው ስድስተኛው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ላይ የምንመለከተው ይሆናል። ይህንን ክልሎች በደስታ መቀበላቸውም ስፖርቱን ለማሳደግ አንድ እርምጃ እንደሆነ ታምኖበታል።

የዊልቼር ቅርጫት ኳስ በአገራችን ከተጀመረ ጥቂት ጊዜ ይሁነው እንጂ በዓመት አንድ ጊዜም ቢሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ውድድሮችን ያስተናግዳል። ይህም የዓለም አካል ጉዳተኞች ቀን የሚከበርበትን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ትንሿ ስቴድየም የሚካሄደው ውድድር ነው። ይህ ውድድር ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ ከኅዳር አስራ ስምንት ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን ነገ ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ሲከበር የሚጠናቀቅ ይሆናል። በዚህ ውድድር በወንዶች አምስትና በሴቶች አራት ተሳታፊዎች ተገኝተውበታል። በወንዶች አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ ክልሎችና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም አዲስ ጉዞ የአካል ጉዳተኞች ማህበር በተጋባዥነት ተሳታፊ ሆነዋል። በሴቶች ደግሞ ኦሮሚያና አማራ ክልሎች፣ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም አዲስ ጉዞ ተሳታፊ ናቸው።

 

ቦጋለ አበበ

 

 

Published in ስፖርት
Saturday, 02 December 2017 20:50

የቡጢ ንጉሡ አይረሴ ታሪኮች

መሐመድ አሊ የቦክስ ብቻም ሳይሆን የነፃነት ተፋላሚ መሆኑ ይታወሳል፤

 

የምን ጊዜም የቦክስ ስፖርት ንጉሡ መሐመድ አሊ የዓለም የቦክስ ቻምፒዮንና ታላቅ የቡጢ ተፋላሚ ብቻ አልነበረም። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፤ የጥቁር ህዝቦች ሰንደቅ፤ በመላው ዓለም በስፖርትና በታላቅ ስብዕና ተምሳሌትም ጭምር ነው። ብዙዎች ቦክስ ስፖርት ሳይሆን የጥጋበኞች ድብድብ አድርገው ከመሳል አስተሳሰብ አውጥቶ የቦክስን ስፖርት ጥበባዊ ገፅታ በማላበስ ተወዳጅና አሁን ላይ በዓለማችን በአንድ ጊዜ በርካታ ሚሊየን ዶላሮች የሚያሳቅፍ ግንባር ቀደምት ስፖርት እንዲሆን ተፅዕኖውን አሳርፏል። ሙዚቀኛም ሆኖ ለሂፕሆፕና ራፕ የሙዚቃ ስልቶች ጉልህ ሚና ተጫውቷል። በቦክስ ስፖርት ታሪክ የምንጊዜም ምርጥ ቦክሰኛ የተባለውም በተለያዩ የቡጢ ፍልሚያዎች ዘመን የማይሽራቸው ገድሎችን በማስመዝገብ ነው። መሐመድ አሊ የቦክስ ጓንቱን ሰቅሎ ስፖርቱን በቃኝ ብሎ ከተሰናበተ ከሦስት ዓመታት በኋላ እኤአ በ1984 ከስፖርቱ ልምድ ጋር በተያያዘ ፓርኪንሰንስ በተባለ በሽታ ተይዞ ነበር፡፡ ለሰላሳ ሁለት ዓመታት ከዚህ ህመሙ ጋር ሲታገል ቆይቶ ከሁለት ዓመት በፊት በሰባ አራት ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

መሐመድ አሊ ወደ ቦክስ ህይወት የመጣበት አጋጣሚ አስገራሚ ነው። የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ በነበረበት ወቅት ብስክሌቱ ተሰርቆበት በሊውስቪል ኬንታኪ ለሚገኝ ጆ ማርቲን ለተባለ ፖሊስ አመለከተ፡፡ «የሰረቀኝን ባገኘው ልክ አገባው ነበር» ብሎም ምሬቱን ይገልፃል፡፡ የቦክስ አሰልጣኝ የነበረው ፖሊስ ትንሹን መሐመድ ራሱን እንዴት ከጥቃት መከላከል መማር እንዳለበት መከረው፡፡ የተወሰኑ ስልጣናዎችን ሲወስድ ቆይቶም ብስክሌቱ ከተሰረቀች ከስድስት ሳምንታት በኋላ በሰፈሩ በአንድ አማተር የቦክስ ግጥሚያ ላይ ተሳተፈና በነጥብ አሸናፊ መሆን ቻለ፡፡ ይህች አጋጣሚም በዓለም ለገነነበት ስፖርት የመሰረት ድንጋይ ነች።

መሐመድ የትውልድ ስሙ ካሴስ ክሌይ ቢሆንም በ19ኛው ክፍለ ዘመን ባሮችን ነፃ ለማውጣት በታገሉ ታላቅ ሰው መታሰቢያነት የወጣለት ስም ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ከባድ ሚዛን ቻምፒዮን ከሆነ በኋላ በማግስቱ ስሙን ለመቀየር ወሰነ፡፡ የነፃነት ታጋዩን ማልኮለም ኤክስ ከጎኑ አድርጎ በሰጠው መግለጫ «ዘ ኔሽን ኦፍ ኢስላም» የተባለውን ተቋም መቀላቀሉን በማሳወቅ የባርያ ስም ይለው የነበረውን ካሴስ ክሌይ በመቀየር በቀድሞ ስሙ ላለመጠራት ወሰነ። በወቅቱ «ኔሽን ኦፍ ኢስላምን» ይመራ የነበረው ኤልጅያህ መሃመድ እኤአ በ1964 ላይ መሐመድ አሊ የሚለውን ስም ካወጣለት በኋላ እሱን በማፅደቅ እስከ ህይወት ዘመኑ መጨረሻ ተጠራበት።

ለሃያ አንድ ዓመታት በፕሮፌሽናል ቦክሰኛነት በርካታ የቡጢ ፍልሚያዎችን ከአሜሪካ እስከ አፍሪካ እንዲሁም ሌሎች ዓለማት ላይ የተፋለመው መሐመድ አሊ ለሦስት ጊዜ የዓለም ከባድ ሚዛን ቻምፒዮን ሆኗል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም የከባድ ሚዛን ሻምፒዮን ለመሆን የበቃውም የሃያ ሁለት ዓመት ወጣት እያለ ነው። ዓለም አቀፍ ደረጃ ባላቸው ፕሮፌሽናል የቦክስ ግጥሚያዎች ላይ ስልሳ አንድ ጊዜ ተሳትፎ ሃምሳ ስድስቱን ማሸነፍም ችሏል። ከእነዚህ ድሎቹም ሰላሳ ሰባት ያህሉን ተጋጣሚዎቹን በበቃኝ በመዘረር ነው። አስገራሚው ነገር በሰላሳ አንድ ተከታታይ የቦክስ ግጥሚያዎች ሳይሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሸነፈው የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ፍልሚያ በተባለው ግጥሚያ በጆ ፍሬዘር ነበር፡፡ በፕሮፌሽናል የቦክሰኛነት ዘመኑም ሽንፈትን የቀመሰው አምስት ጊዜ ብቻ ነው። የመጨረሻውን ፍልሚያም እኤአ በ1981 ከትሬቨር ቤሪቢክ ጋር በማድረግ ስፖርቱን በቃኝ ብሏል።

አሜሪካ በቬትናም በ1970ዎቹ መጀመሪያ ያደረገችውን ጦርነት በመቃወሙ ለሦስት ዓመታት ከፕሮፌሽናል ቦክስ ውድድሮች ታግዶ የቆየው መሐመድ አሊ እገዳው በተጣለበት ወቅት ከአስር የማያንሱ የዓለም ከባድ ሚዛን ቻምፒዮናዎች ባያመልጡት አሁን ካሉት የበለጠ በርካታ ክብሮችን መጎናፀፍ ይችል ነበር። በዚህም ከሰማንያ ሚሊየን ዶላር በላይ ሀብት ማፍራት ችሏል። ለዚህ ሀብቱም ምንጭ ስፖርቱን ከተሰናበተ ወዲህ ግንባር ቀደም ተዋናዮቹ ስሙንና ምስሉን የሚጠቀሙ ከአርባ በላይ ኩባንያዎች ናቸው። ታሪካዊው ኢትዮጵያዊ አትሌት አበበ ቢቂላ በ1960 የሮም ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ለጥቁር ህዝቦች የመጀመሪያውን የማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ሲያስመዘግብ መሐመድ አሊም በቦክስ የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቆ ነበር። ሁለቱ ታሪካዊ የጥቁር ህዝቦች ከዋክብት ፊርማቸውን ተለዋውጠውም ነበር። ይሁንና መሐመድ አሊ ይህን የወርቅ ሜዳልያውን ለአገሩ ከማበርከት ይልቅ በሊውስ ቪል ግዛት በሚገኘው የኦሃዮ ወንዝ ጨምሮታል። ሜዳልያውን ለአሜሪካና ለትውልድ ከተማው ሊውስ ቪል ቢቀዳጅም በርገር የመግዛት መብት ባለመኖሩ ተቃውሞውን ለመግለፅ ነበር ይህን እርምጃ የወሰደው።

1996 አገሩ አሜሪካ ባስተናገደችው የአትላንታ ኦሊምፒክ ችቦውን እንዲለኩስ ከመደረጉ ባሻገር ወንዝ የጨመረው የወርቅ ሜዳልያ ምትክ ሌላ ሜዳሊያ በአንገቱ ተጠልቆለታል። በ1980 በላስቬጋስ በተካሄደ የቡጢ ፍልሚያ በቴክኒካል የበቃኝ ውጤት ቢሸነፍም መሐመድ ትልቁን ክፍያ ስምንት ሚሊየን ዶላር ያፈሰው በዚያ ውድድር ነው። «ራምብል ኢን ዘ ጃንግል» በተባለውና እስካሁንም ከስፖርት ቤተሰቡ አዕምሮ በማይጠፋው በአፍሪካ ምድር በተካሄደው ፍልሚያ መሐመድ አሊ ምን ጊዜም ይታወሳል። እኤአ በ1974 መሐመድ አሊ በሰላሳ ሁለት ዓመቱ ሽንፈትን አይቶ ከማያውቀው ከሃያ አምስት ዓመቱ ጆርጅ ፎርማን ጋር በኮንጎ ኪንሻሳ የቡጢ ፍልሚያ ገጥሞ ነበር። በወቅቱ የኮንጎ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሞቡቱ ሴሴኮ ለሁለቱ ቦክሰኞች በኪንሻሳ ከተማ እንዲጫወቱ በነፍስ ወከፍ አምስት ሚሊዮን ዶላር ከፍሏቸው ነበር፡፡መሐመድ አሊ በውድድሩ ስምንተኛ ዙር ላይ በዝረራ ቢሸነፍም ከወጣት ተፋላሚው ጋር ያደረገው እልህ አስጨራሽ የቡጢ ፍልሚያ እስካሁንም ከህሊና የሚጠፋ አይደለም። በ1970 የዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ መታሰቢያ ሽልማት የተቀበለው መሐመድ አሊ፤ የዓለም አቀፋዊ ወዳጅነት ተምሳሌት ሆኖም ያውቃል። የተባበሩት መንግሥታት የሰላም መልዕክተኛ ሆኖም ከ1998 እስከ 2008 በታዳጊ አገራት በመዘዋወር አገልግሏል። በህይወቱ ዙሪያ በሚያተኩሩ ጥናታዊና የሙሉ ጊዜ ፊልሞች የሰራ ሲሆን በተለይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀውና ዘ ግሬተስት በተባለ ፊልም ላይ ተውኗል፡፡ የህይወት ታሪኩ ላይ በማተኮር ከተሰሩ ፊልሞች የኦስካር ሽልማት በጥናታዊ ፊልም ዘርፍ ያገኘው «ዌን ዊ ዌር ኪንግስ»ና ዝነኛው የሆሊውድ ተዋናይ ዊል ስሚዝ በመሪ ተዋናይነት የተጫወተው «አሊ» የተባሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ታላቁን የደቡብ አፍሪካ ነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ከእስር እንደተፈቱ በአካል ተገኝቶ ደስታውን ለመግለፅ መሐመድን የቀደመው የለም። በአካል ካገኛቸው ታላላቅ መሪዎች የእንግሊዟ ንግሥት ኤልሳቤጥ፤ የሮማው ሊቃነ ጳጳስ ፖፕ ጆን ፖል፤ የኩባው መሪ ፊደል ካስትሮ እንዲሁም የኢራቁ ሳዳም ሁሴን ይገኙበታል፡፡ አይም ዘ ግሬተስትና ስታንድ ባይ ሚ ከዘፈን ሥራዎቹ መካከል የሚጠቀሱት ናቸው፡፡ በንግግር ችሎታው፤ በልዩ የግጥም ስንኞቹም ተወዳጅነት ያተረፈ መሐመድ አሊ ነው፡፡ «በማይሞት እምነትና ፍቅር ዓለም የተሻለ ዓለም መፍጠር እንደሚቻል አሳይቶናል፡፡ ሁሌም ቻምፒዮን ነው»፡፡ በማለት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ በርካታ የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪና ታላላቅ ሰዎች መሐመድን ወደማይመለስበት ሸኝተውታል።

 

ቦጋለ አበበ

 

 

Published in ስፖርት
Saturday, 02 December 2017 20:43

ሰዎች ያወራሉ

ወጋ ወጋ በነገር

«ቶሎ እንውጣ ውዴ...እንዳያመልጠኝ» አለች ከጎኗ የተቀመጠውን ባሏን በተማጽኖ እያየችው። አስተያየቷን አላየም እንጂ ያለአንዳች ማመንታት ይነሳ ነበር። ይብሱኑ «ምን አልሺኝጠየቃት። አልሰማትም ይሁን ወይ አልገባውም ግልጽ አይደለም። የተመገበው የጾም ይሁን የፍስክ ምግብ፥ የለመዱ ጣቶቹ ስንጥር ይዘው ጥርሶቹን እየጎረጎሩ ነበር።

«እንሂድ ነው የምልህ ውዴ፤ ያመልጠኛል» በተማጽኖ ፊት እያየችው እንደሆነ አሁንም አላስተዋለም። ይልቁኑ አጠራሯ ከመቼ ጀምሮ እንደተቀየረ ለማስታወስ እየሞከረ ሳይሆን አይቀርም። «ምንድን ነው የሚያመልጥሽጠየቃት። «...ዕቃ የማጥበው አለኝ» አለችው ደንገጥ ብላ። የትም ትሁን የት ልቧ ከአንድ የቴሌቭዥን ስርጭት ላይ አልነቀል እንዳለ የሚያውቅ ይመስላል። «በይ ተነሽ እሺ እንሂድበስጨት ብሎ ስንጥሩን ወርውሮ ተነሳ።

«ማርያም ትስጥልን፤ ዓመት ዓመት ያድርስልን...» ሊወጡ ሲነሱ በቅርብ ርቀት ያዩት እኔን ነበርና ስንብትና ምርቃት አስረከቡኝ። ተቀብዬ ሸኘሁ። መቼም የባልና የሚስት ወሬ ለምን ትሰሚያለሽ አትሉኝም አይደለ? ሚስጥር አላወሩ? ሚስጥር ቢሆን እኔስ መች እነግራችሁ ነበር?

እነሱን ሸኝቼ ስመለስ ጆሮዬ ሌላ ጨዋታ ላይ አረፈ። «አሁንማ ሞልቶ፤ መልሶ ልጥፋ ካላለ በቀር» አሉ አንዲት ሴት ፊታቸው የቀረበውን ጠላ ፉት ብለው አፋቸውን እየጠራረጉ። «ጉደኛስ እነዛ የአንቺ ጎረቤቶች! ሆሆይ! ቤተሰብ አሰልፈው ነውኮ የገዙት? መቼም እንደዝንጅብል ጓሮ ቆፈር ቆፈር አድርገው ሳይቀብሩት አይቀሩም» ሞቅ ያለ ሳቅ! የስኳር ነገር ለካ ገና አልወጣልንም!

«ውሃ ታመጭልኝ የኔ ልጅ» ድንገት ጆሮዬን ልኬ እየሰማኋቸው እንደነበር ያወቁ የሚመስሉ ሴት አናገሩኝ። «ወዬ! እሺ...» ፈጠን ብዬ ትቻቸው አለፍኩ። ወደቧንቧ አልሄድኩም፤ ውሃ አልነበረችም። ከታሸጉ ውሃዎች መካከል አንድ ሁለት አወጣሁና ወስጄ ከከበቡት ጠረጴዛ ላይ አስቀመጥኩላቸው። «ኧረ እቴ! እኛስ በደኅና ጊዜ ሻይና ቡናውን ቀንሰናል፤ ዘወር ዘወር ስል ዘመድም ጎረቤትም ጋር ከጠጣሁ አነሰጆሮዬ አያርፍ ሰማኋቸው።

ቤታችሁ እንግዳ ሲበዛ መረጋጋት የሚባል ነገርን ማሰብ ከባድ ነው። ከርሞ ከርሞ ያገኛችሁትን ሰው ሳይቀር በወጉ ላታወጉ ትችላላችሁ። እንደው ወዲያ ወዲህ ብቻ! ሆቴሎችና ሻይ ቤቶች ውስጥ መስተንግዶ የሚሠሩ ሰዎች አሳዘኑኝ። እዛም እዚህም ሲጠሩ፤ ድግስ እንዳለባት ወይዘሮ ሁሌ ሽር ጉድ እንዳሉ።

«ምን ይጨመር? ወጥ? እንጀራወደአንዱ ጠረጴዛ ጠጋ ብዬ ጠየቅሁ። «ምንም...ሁሉም አለ» አለኝ አንዱ። ቀሪዎቹ ልብ ብለው የሰሙኝ አይመስልም። «አብዛኞቹ ተዘግተዋልኮ። ለኛማ ማን ይነግረናል? በአንድ በኩል ማኅበራዊ ድረ ገጽ ውሸት ነው ይባላል። ግን ቢያንስ አንድ እውነት መነሻ እንደሚሆን ታያላችሁ። እውነቱ ደግሞ አይነገረንም» አለ አንዱ በተማረረና በሰለቸ ድምጽ።

«እኔስ አስቀድሞ ልጄን ያልላኩት ይህን ፈርቼ አይደለ? መግቢያ መውጫው ቢዘጋ በየት በኩል ላመጣው ነውአለ ሌላው። «የኔም ልጅ ያው ኢትዮጵያዊ ነው፤ በወንድሞቹና እኩዮቹ ላይ መጥቶ በእሱ ላይ ምን ሊቀር ነው? ሄዶ የሚሆነውን ይይ ብዬ ነበር፤ እናቱ ከለከለች እንጂ» አለ ከመካከላቸው በእድሜ ጠና ያለ ሰው። «እኔ ራሱ ይኸው ተዘግቷል ብላ ልጄ መጥታ፤ ማን፣ መቼ፣ እንዴት ትምህርት መጀመሩን እንደሚነግረን አናውቅም።...ምን እንደሚሻል

በድንገት ስሜ ሲጠራ ሰማሁ። እንግዶቹ ጨዋታቸውን ስሰማ መቆየቴን ሳያስተውሉ ከአጠገባቸው ራቅሁ። ከተጠራሁበት የሚጨመርና የጎደለውን እንዳሟላ ትዕዛዝ ተቀብዬ መልሼ ወደወጥ ቤት አመራሁ። ደጋግና አሁንም ድረስ ጎረቤት መተጋገዙን እንዳልተዉ መመስከሪያ የሚሆኑ ጎረቤቶቻችን ወጥ ቤት ተቀምጠው፤ ከስራቸው ጠላ ይዘው የሹክሹክታ ጨዋታ ይዘዋል።

«ኧረ የፍስክ ይሻላል። አስቡት እስቲ! ሽንኩርቱ፣ ጎመኑ፣ ምስሩ፣ አተሩ፣ ቀይ ስሩ፣ ድንቹ፣ ሽሮው፣ ሱፉ፣ ፎሶልያው፣ ካሮቱ...ከውጪ የሚገባ ይመስል ሁሉም ውድ ሆኗል። እና የፍስክ አይሻልምትጠይቃለች። ሌላዋ ቀበል አድርጋ፥ «አይ! እንዴት እንደሚገፋልንም እንጃ...ልጄ ምስር ይወዳል፤ ምስር ዋጋው ተወዷል...ስንቱ ያሳስበናል እናንተዬ! እስቲ ከምስር ወጥ አድርጊና ጎረስ ላድርግ፤ መች ከብፌው ምግብ አነሳሁ...»

መመገቢያ ሳህን ልታነሳ ስትነሳ ተያየን፤ «ምን ልስጥሽ እናትዋ! ምን ጎደለጠየቀችኝ። «እንጀራ የተቆረጠ ካለ ተፈልጎ ነው። አለ የተቆረጠበፍጥነት እጅ በእጅ ተጋግዘው በርከት ያሉ በስርዓት የተቆራረጡ እንጀራዎችን ሰፋ ባለ ሳህን ደርድረው ሰጡኝ። «የሚጠጣ ነገር ላምጣላችሁዝም ብዬ መውጣቱ ልክ ስላልመሰለኝ ጠየቅሁ። «ምንም የኔ እናት! ምንም አያስፈልግ...የጎደለ ወጥ ካለ ሳህኑን ይዘሽ ነይ ባይሆን» ወጣሁ።

«በዓሉ አርብ ቢውል እንዴት ጥሩ ነበር። ቅዳሜ ቅዳሜ ነው። እሁድም ያው እሁድ ነው። ጥሩ ይሆንልን ነበር» አለ ደረቅ እንጀራ ያቀረብኩለት ወጣት እንግዳ። «አሁን እንዲህ ጥግብ ተብሎ ነገ ሥራ ይገባልተለቅ አድርጎ ጎረሰ። ቁጣውን ምግቡ ላይ ያሳረፈ መሰለኝና ምግቡ አሳዘነኝ። «አንቺ አትበይም እንዴበፍርሃት ስታየው የቆየች የምትመስል ሴት ከጎኑ ተቀምጣለች። «ብይ እንጂ! ምን ላምጣአልኩኝ እኔም፤ የአስተናጋጅነት ስልጣኔን ለመጠቀም።

«ምንም...አመሰግናለሁ፤ ሁሉም አለ» አለች። «አሁን ነገ ጠዋት ፊርማ ይነሳል ብዬ በጠዋት ልነሳ ነው? በዛ ላይ ትራንስፖርት፣ በዛ ላይ መንገድ መጨናነቁ፣ በዛ ላይ ቁርስ የት ልበላ ነው? ደግሞ...» እጁ ራሱ አፉን ሊያዘጋው የፈለገ ይመስል ጉርሻውን ላከበት። «አሁን በዓሉ ነገ ቢሆን ምን ነበረበትይህ እንግዲህ ጉርሻውን በአፉ እንደያዘ የተናገረውን ኩልትፍትፍ ያለ አማርኛ ሳቃናው ነው።

«ቡና ፈልቷል፤ አንዳችሁ አስይዙልኝ እያለች ነው» ወንድሜ በጆሮዬ ሹክ ሲለኝ ቡና የተቀዳባቸውን ሲኒዎች ይዤ ለሚጠጡት ማድረስ ጀመርኩ። «የደግነታችን ብዛት ንጹህ ቡና ለውጪ ገበያ ነው የምንልከው፤ እነሱ በዛኛው ቡና ተመራምረው ጥሩ ነው ጥሩ አይደለም ሲሉን እኛ በዚህኛው እየመሰለን...» አለ፤ የመጀመሪያውን ሲኒ የተቀበለኝ ሰው። «ምን አለበት ታዲያ፤ የውጪ ምንዛሬ ያስገኛል፤ እስክናድግ ድረስ የምንከፍለው መስዋዕትነት ነውአለ ሌላው ፈገግ ብሎ። ይህን የተናገረው ሰው ቡና አለመጠጣቱ ገረመኝ።

«ቡናስ ለትርፍ ነው፤ የጤፉም ማኛ እየተላከ ብጣሪውን መብላት እንዳትጀምር ፍራሌላው ቀልድ የተናገረ መስሎት ቀድሞ ሳቀ። ሁሉም በሱ ልክ አልሳቁም፤ ግን ፈገግ አሉለት። «እኔ ባለሙያ ሚስት ስላለችኝ፤ ቡናው ገለባ ይሁን የተጣራ ሳላውቅ ነው የምጠጣው። አንደኛ ደረጃው ምን እንደሚመስል ሳላውቅ ምን አመራመረኝ...ያለውን ያጣፍጥልን አቦሌላው በክብርና በጥንቃቄ ሲኒውን ተቀበለኝ።

ወደሌላ ጠረጴዛ አቀናሁ። «ነዳጅማ አይኖርም! እንኳን ነዳጅ ገና እንደ ስኳር ዘይትም ጠፍቶ በቂቤ መብላት እንጀምራለን!»...ሳቅ በሳቅ። «የምሬን ነው፤ እኔ የዶላር መጨመር አሁን ነው የሚሰማን ባይ ነኝ። ከዚህ በኋላ ህዝቤ ተዘጋጂ! ሁላችንም እኩል የምንሆነው በሞትና በዶላር መጨመር ነው» ሌላ ሳቅ! ነገሩ ማሳቁን እንጃ ግን የሰዎቹ ሳቅና አሳሳቅ እኔንም አሳቀኝ።

ሰፊ ሊባል በሚችለው ጊቢ ውስጥ ሰብሰብ ብለው በቡድን በቡድን የተቀመጡትን እንግዶች ሳስተናግድ አብሬ ጆሮዬን ጣል ማድረጌ ትዝብት ውስጥ ከትቶኝ እንደሆነ እንጃ! ግን ሰው ስለምን ያወራል የሚል ጥናት ለማድረግ ናሙና ከተፈለገ አንድ መለስተኛ ድግስ መደገስ ብቻ በቂ እንደሆነ መናገር እችላለሁ።

መቼም ሰው ሚስጥር ቢሆን መስኮቱን ዘግቶ፣ በሩን ጠቅጥቆ ያወራል እንጂ ድግስ ቤት ሆኖ አያወራም። ስለዚህ መስማቴ ክፋት ላይኖረው እንደሚችል ልከራከር እችላለሁ። ደግሞ የገዛ እንግዶቼን ጨዋታ ብሰማስ ምን አለ? ዓይን ብቻ አይደለም አትይ የማይባለው፤ ጆሮም አትስማ አይባልምኮ!

አንድ ሲኒ ቡና ቀረች። ብቻዋን እንዳትመለስ ብዬ ወደ አንዱ ጠረጴዛ ቀረብኩ። «ቡና ትጠጣላችሁእርስ በእርስ ተገባበዙና ሌላ ተቀድቶ እስኪመጣ ድረስ አንዱ እንዲጠጣ ተፈረደለት። «እንዴት ነሽ ታድያ? ሥራ ሁሉ ሰላምጠየቀኝ ቡናውን እያማሰለ። «ሁሉ ሰላም አለን ይመስገን...» ምላሼ ነበር። «ምንድን ነው ጋዜጣችሁ ግን መጠኑ አይቀነስም እንዴ?»... ሳቅ አልኩና የተቀዳ ቡና ላምጣ መጣሁ ብዩ ሄድኩ። የጨመረ ነገር በበዛበት ዘመን ይቀነስ የሚባል አንድ ተገኘ ይሆን?፤ ሰላም!

 

ሊድያ ተስፋዬ

 

 

 

 

Published in መዝናኛ

 

ኢትዮጵያውያን ጥቃት አንወድም፤ኢትዮጵያዊ ጥቃት አይወድም።እሱም ነው ለዘመናት አስከብሮ ያኖረን።ጥቃት የማይወድ ህዝብ ራሱን ብቻ ሳይሆን አገሩን ያስከብራል።ጥቃት የማይወድ ሰው ክብር አለው፤ አስቀድሞ ራሱ ያከበረውን ነገር ነው አክብሩልኝ የሚለውና የሚያስከብረው።ለዛም ነው «ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ» ይሉትን ብሂል ሲነገር፤ ሲቀባበል የኖረው።

ይህ ማንነት ይሠራ ይሠራና ሴቶች ላይ ሲደርስ የት እንደሚገባ እንጃ! ይጠፋል። ጥቃት ከሚፈጽም ወንድ ጀምሮ ጥቃቱን አይቶ፣ አሳልፎ ዝም እስከሚሉ እናትና ጉዳዩን የአንድ ሰሞን ወሬ አድርጎ እስከ ሚያንሾካሹከው ማኅበረሰብ ድረስ፤ ኢትዮጵያዊ ጥቃትን ያለመውደዱ ነገር የቱ ጋር እንደሚገለጽ ግራ ይገባል። ይህ ባይሆን ኖሮማ ስንቱን አስጸያፊና አስከፊ፤ በሴቶች ላይ የደረሰ ጥቃት ደርሶ ባልሰማን ነበር።

ኅዳር 16 ቀን 2010.ም የጸረ ጥቃት ዘመቻ ተከፍቷል።ይህም በአገራችን ለ12ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ 26ኛው ዘመቻ ነው። ታዲያ ይህ እስከ ታኅሳስ 1 ቀን 2010.ም የሚዘልቀው ዘመቻ መሪ ሃሳቡ «በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለማስወገድ የወንዶች አጋርነትን ማጠናከር» የሚል ነው።

ይህ ምን ማለት ነው? ጥቃትን ለማስወገድ ወንዶች አጋርነታቸው ተጠየቀ ማለትስ ምን ማለት ነው? ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ኤልያስ የአዲስ አበባ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ዋና ኃላፊ ናቸው። ለዚህ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል፥ «ሴቶች የማኅበረሰቡ አባል ናቸው። የሚኖሩበት የተለየ ዓለም የለም። ነገር ግን በሴቶች ላይ የሚደርስን ጥቃት በአጋሮቻችን በተለይም በወንዶች አጋርነት ነው መከላከል የምንችለው። ወንዱ ብቻ ጥቃት ያደርሳል የሚል ነገር ግን የለም»ይላሉ።

በቢሮው የስርዓተ ዖታ ማስረጽ ቡድን መሪ የሆነችው ወይዘሪት ሰብለ ሽፈራው በበኩሏ የስርዓተ ጾታ እኩልነት አለ ለማለት እንደማይቻል ትገልጻለች።እንደ አዳጊ አገር ኢትዮጵያም ሆነች የምትገኝባት አህጉር አፍሪካ ከዚህ ችግር ነጻ አይደሉም።የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማምጣት ታሪካቸው ዝቅ ተደርገው ሲቀመጡ የኖሩ ሴቶች ለብቻቸው የሚያደርጉት ጥረት ብቻውን በቂ ሊሆን አይችልም- እንደ ሰብለ ገለጻ።

እንደ አገር አለን ብለን የምንኮራበት የመተጋገዝ ባህልም በዚህ ጉዳይ ላይ ጎልቶ መታየት እንዳለበት ትናገራለች። ከዛ ባሻገር የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማምጣትና የወንዶች አጋርነትን ለማጠናከር አመለካከት ላይ በስፋት መሥራት እንደሚገባም ነው ባለሙያዋ የምታስረዳው።

የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊና ባለሙያ የሆኑ ሴቶች ይህን አስተያየት ከሰጡን በኋላ ወደ ወንዶቹ አቀናን። በእርግጥ ቢሮው ለጸረ ጥቃት ዘመቻ በጀመረው እንቅስቃሴ መሪ ሃሳቡ መካከል «የወንዶችን አጋርነት ማጠናከር» የሚል ሀረግ ያስገባው ያለምክንያት ነው ወይ? ወንዶቹስ ምን ይላሉ? አጋር ለመሆን ዝግጁ ናቸው? ከሴቶችስ ምን ይጠበቃል ይላሉ?

ለነዚህ ነጥቦች አስተያየት የሰጡንን ሁለት ወጣቶች በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ባህል ማዕከል አዳራሽ ውስጥ አገኘን። በማዕከሉ ኅዳር 19 ቀን 2010.ም አንድ ዝግጅት ነበር። ይህም ጥቃትን ለመከላከልና የስርዓተ ጾታ እኩልነት ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ኪነጥበብ ቁልፍ መሣሪያ ሊሆን ስለመቻሉ የተነሳበትና ስነጽሑፋዊ ዝግጅቶች የቀረቡበት መድረክ ነበር። 16 ቀናት ከተያዘለት የጸረ ጥቃት ዘመቻ መርሃ ግብር መካከል ይገኝበታል።

«መጀመሪያ አሉታዊ የሆነውን አመለካከት ወደ አዎንታዊ ማምጣት ነው የሚያስፈልገው» ያለን ወጣት ክብሮም መልካሙ ነው። ወጣት ክብሮም በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የኤሌክትሪካልና ኮምፕዩተር ምህንድስና አራተኛ ዓመት ተማሪና በዛው ዩንቨርሲቲ የወንዶች አጋርነት የተባለ ቡድን ፕሬዚዳንት ነው።

እንደ እርሱ ያሉ የግቢውን ወጣት ተማሪዎች ያቀፈው ይህ ክበብ ዓላማውን ያደረገው በስርዓተ ጾታ ዙሪያ የሚንጸባረቀውን አሉታዊ አመለካከት መለወጥ ላይ ነው። በንግግሩም፥ «ለአንዲት አገር ጤናማ ትውልድ ያስፈጋል ሲባል በአካል ብቻ ሳይሆን በሞራል/በአመለካከት ጭምር ነው» አለ። በዚህም መሰረት አንዲት ሴት በወንድ ሊደርስባት ከሚችል ጥቃት መጠበቅ አለባት፤ ይህ ጤናማ አመለካከት ነው።

ክበቡ በትምህርት ተቋሙ የወንዶች አጋርነት በሚል አሃዱ ብሎ ከጀመረ ሶስት ዓመታት ተቆጥረዋል። ታዲያ ወንዶች በአጋርነት በሚሳተፉበት በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ሴቶችም በአባልነት ይገኛሉ። «የአጋርነት ክበብ ላይ የምንሠራው በተለይ ሴቶች ላይ በአመለካከት ምክንያት ያለውን ጫና ለመቀነስ ነው» ብሏል። ይህም በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሁሉ እንዲስፋፋ ብሎም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሳይቀር እንዲለመድና ተግባራዊ እንዲሆን ጥረት እንደሚያደርጉ ነው ወጣት ክብሮም የሚናገረው።

አቶ መኮንን ማናዬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ፍላጎት ድጋፍ ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ ባለሙያ ነው። «ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ እንዲሉ ለብቻ ተሠርቶ ውጤታማ መሆን አይቻልም። አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብምና አጋርነት በጣም አስፈላጊ ነው» ይላል፤ የአጋርነትን አስፈላጊነት ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ።

ከሴቶች ጉዳይ ጋር በተያያዘም ይሄው መሆኑን ነው የሚናገረው።እንደ አቶ መኮንን ከሆነ ሴቶች ለብቻቸው በሴቶች ጥቃት ላይ ቢሮጡ የሚያመጡት ውጤት የሚጠበቀውን ያህል አይሆንም።ስለዚህ ወንዶችም በዚህ ጉዳይ ላይ ማገዝ አለባቸው። ከዚህ ባሻገር ሴትነት ላይ አካል ጉዳት ሲጨመር ችግሩን ከፍ ያደርገዋልና በአመለካከት ካለው ክፍተት ጋር ሲዳመር ችግሩን ይበልጥ ፈታኝ ስለሚያደርገው ወንዶቹ የግድ አብረው መተጋገዝ እንዳለባቸው ሃሳቡን ገልጿል።

«ሴቶች ወደ ውጤት እንዳይመጡ እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮችን መንቀል የወንዶች የሁላችን ሥራ ነው» ሲልም ይናገራል።እነዚህ ወንዶች «እኔ በሴቶች ላይ ጥቃት አላደርስም።ጥቃት ሲደርስም ከሴቷ ጎን በመቆም ጥቃቱን እከላከላለሁ።ጥቃቱን ከሚከላከሉት ጋር በመቆም አጋርነቴን እገልጻለሁ» ሲሉ ፊርማቸውን ያኖሩ፤ ቃላቸውንም የሰጡ ናቸው።

አቶ መኮንን አንድ ሃሳብ እንዲህ ሲል አቀበለን፥ «ሴት ልጅ ከዘጠኝ ወር እርግዝና፤ ከድካምና ከብዙ ምጥም በኋላ ልጅ ትወልዳለች። አንዳንዴም በዚህ ሂደት ህይወቷ ሊያልፍ ይችላል። እንዲህ መስዋዕትነት ከፍላ የወለደችው ልጅ በባሏ ስም ሲጠራ ግን አይከፋትም። በዚህም ፍቅሯን ታሳያለች። ወንዶች ይህን እንኳ ልንረዳ ይገባል»ይላል።

መቼም በአንድም ይሁን በተለያየ አጋጣሚ ዝቅ የተደረገን ሰው መንገድ ለማቃናት አጋር እሆናለሁ ያለ ሰው ብቻውን ለውጥ አያመጣም። አጋርነቱን ያገኘውም ሊያደርጋቸው የሚገቡ ጥረቶች አሉ። ታድያ እነዚህ ወንዶች ከሴቶችስ ምን ይጠበቃል ይላሉ? «ከሴት የሚጠበቀው መጮህ ነው። 'ባለቤት ካልጮኸ...' እንዲሉ» ያለን አቶ መኮንን ነው። ያም ብቻ ሳይሆን «እንችላለን» ከሚለው ወሬ በዘለለ በተግባር ማሳየት፤ በኃላፊነት ቦታ እንዲሁም በትምህርታቸው ውጤታማ ሆኖ መገኘት ይጠበቅባቸዋል ባይ ነው።

ወጣት ክብሮም በበኩሉ በክበቡ የወንዶች አጋርነት ከሴቶች ግልጽነትና አጋርነትን ለመቀበል ዝግጁነት መኖር አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻል። «አንድ ነገር ተከስቶ እኛ አጋር ነን ስንል ሌላ ነገር መስሏቸው መረጃ ይደብቃሉ። ዝም ይላሉ፤ ይፈራሉም። ቢቻል አባል ሆነው በደንብ መሳተፍ አለባቸው። ፈቃዳቸውን ማሳየት መቻል አለባቸው» ሲልም ይናገራል።

ወንዶቹ የሚሉት እንዳለ ሆኖ በማንኛውም ሁኔታ ግን ሴቷ በራሷ ጠንካራ መሆን ይጠበቅባታል። ወይዘሪት ሰብለ ይህንኑ ትላለች፥ «ሴቷ በራሷ ልትተማመን፤ አትችልም የሚለውን ሰብራ መውጣት አለባት። የተሰጧት መብቶች አሉ፤ እነዛንም አውቃ መጠቀም አለባት። ከዛ በተጓዳኝ ለጥቃት አጋላጭ ከሆኑ ነገሮች ራሷን መጠበቅ ይኖርባታል» ባይ ናት።

ወይዘሮ አለምፀሐይ የሴቶችን ጥቃት አቅልሎ ማየት እንደማይገባና በዚህም ላይ ህብረተሰቡ በነቃ ሁኔታ ማየትና ችግሮችን አለመሸከም እንዳለበት ይገልጻሉ። «ምንአልባት አንዳንድ ችላ የሚሉ ፍትህ አካላት ይኖራሉ፤ ግን ተስፋ ሳንቆርጥ ይህንንም ጥሰን ጥቃቱን መከላከል አለብን። ጥቃትን የመከላከል ሥራ የህብረተሰቡ መሆን አለበት» ብለዋል።

እንደማሳያ በዚህች ውስን ቃላትን በምታስተናግድ አምድ ላይ ይህን ቀንጭበን አነሳን እንጂ የተለያየ አስተያየት ሊነሳ እንደሚችል ግልጽ ነው። ዞሮ ዞሮ ግን መግቢያው በየጊዜው በሴቶች ላይ ደርሶ የምንሰማውን ጥቃት፣ በደልና ጉዳት በሴቷ ላይ ላለማድረስ፤ ብሎም ለማስቆምና ይበቃል ለማለት የወንዶች አጋርነት ያስፈልጋል ነው።

ከሴት በቀር ከሌላ የተወለደ የለምና፤ እናቱ ከወለዷቸው ልጆች መካከል ያለችው ሴት ልጅ እህቱ ናትና፤ ልጆችም ወልዶ እንደሆነ ከመካከላቸው ሴት ትኖራለችና፤ ይወዳት፤ ፍቅርንም ተቀብሎ ይሰጣት ዘንድ፤ ሁሉን ትታ ከእርሱ ጋር የሆነች ሚስቱም ሴት ናትና፥ የትኛውም ወንድ የሴቷን ጥቃት ለማስቆም አጋር ሳይሆን አይቀርም። እንደው ሰውነቷ- ሰው መሆኗ ቢቀር ይህ ሁሉ ያስገድደዋል። ቆም ብሎ ይህን እንዲያስብና እንዲያስተውል ብቻ ይጠየቃል። ሰላም!

 

ሊድያ ተስፋዬ

 

 

Published in ማህበራዊ

የኢትዮጵያ ህዝቦች ለዘመናት ተራራ ሆኖባቸው የቆየውን ድህነትን ታግለው ለመጣል፤ ቀጣይነት ያለው ልማትን ለማስመዝገብ ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ፡፡ይህን ራዕያቸውን እውን ለማድረግ ሁሉም የአገሪቱ ህዝቦች የተባበረ ክንድ ያስፈልጋል፡፡ምክንያቱም ህዝብ ለአንድ ዓላማ በአንድ መንፈስ ሲነሳ በአገሪቱ ሰላም ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ሰላም ካለ በአገሪቱ የተጀመረው የልማት እንቅስቃሴ እንዲፋጠን ያደርጋል፡፡የአገር ሉዓላዊነት ይከበራል፡፡ከዚህም ባሻገር የአገር ገፅታን በመገንባት የውጪ ባለሀብቶችን ለመሳብ ያስችላል፡፡

በመሆኑም በአገሪቱ ቀጣይነት ያለው ሰላምና ልማትን ለማስፈን በህዝቦች መካከል የአንድነት መንፈስ መፍጠር ዋናውና ትልቁ ጉዳይ ነው፡፡የኢትዮጵያ ህዝቦች ለብዙ ዘመናት በአንድነት ኖረዋል። በደም፣ በባህልና በሀይማኖት ተቆራኝተዋል፡፡ በተለያየ ጊዜ የአገሪቱን ዳር ድንበር ጥሶ የመጣ ጠላትን በአንድነት የሽንፈት ካባ አከናንበው መልሰዋል፡፡ ይህ የብሔራዊ አንድነት ውጤት ነው፡፡

የኢትዮጵያን አንድነትና እድገት የማይፈልጉ ከውጪም ይሁን በአገር ውስጥ ጥቂት ሀይሎች በህዝቦች መካከል የዘረኝነት አመለካከትን በመዝራት፤ በህዝቦች መካከል የአንድነት መንፈስ እንዲጠፋ በማድረግ አገሪቱን በዘር፣ በጎሳ፣ በብሔር ለመከፋፈልና አንዱን ብሔር በሌላው ላይ እንዲነሳሳ ሲያደርጉና ግጭቶችን ለማነሳሳት ሲሞክሩ ተስተውሏል። በመሆኑም የአገሪቱን አንድነት የማይፈልጉ የጥቂት ሀይሎች አስተሳሰብን ሰብሮ በአገሪቱ የተጀመረውን የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞን ለማስቀጠል ህዝቦቿን በአንድነት ማስተሳሰር ያስፈልጋል፡፡

በቅርቡ በአማራና በኦሮሚያ እንዲሁም በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የህዝቦችን ዴሞክራሲያዊ የአንድነት መንፈስ በማጠናከር በኩል ፋይዳው የጎላ መሆኑን የተለያዩ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱም በአገሪቱ ሰላምና ዴሞክራሲን በማስፈን፣ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና በአገሪቱ ቀጣይነት ያለውን ልማት ለማረጋገጥ ይረዳል ሲሉ ይመክራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፣በክልሎች መካከል የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የአገር አንድነትን ለማጠናከር፣ ለባህል ልውውጥ እንዲሁም ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በማድረግ በኩል ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ይናገራሉ። ግንኙነቱ ግን ፓርቲዎች በሚፈልጉት መንገድ መሆን እንደሌለበት ያስረዳሉ፡፡

እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ እምነት አሁን በክልሎች መካከል እየተደረገ ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መልካም የሚባል ጅምር ነው፡፡ ግንኙነቱ ግን ፓርቲዎቹ በሚፈልጉት መንገድ ሳይሆን ህዝቦችን ሊያገናኝ በሚችልበት መንገድ መሆን አለበት፡፡ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በመድረኩ ላይ ሚናቸውን መወጣት አለባቸው፡፡የአማራና የኦሮሚያ ክልል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የሁለቱ ክልሎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተባለ እንጂ መድረኩን ያዘጋጁት ብአዴን እና ኦህዴድ ናቸው፡፡ፓርቲዎቹ መድረኩን ማመቻቸታቸው ጥሩ ነው።ሆኖም ግን ህዝቡ ሃሳቡን በነፃነት ሊገልፅበት የሚችልበትን መድረክ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ «የክልል ህዝቦች በአንድነት አንድ ራዕይ አለን፣የአንድ አገር ዜጎች ነን፣ሁላችንም በአንድነት ወደፊት እንራመዳለን» የሚለውን ሀሳብ በራሳቸው የሚያቀነቅኑበት ነፃ የሆነ መድረክ መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ይህ ሲባል ግን የአማራና የኦሮሚያ ክልል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በአንፃራዊ የተሻለ ነው፡፡ የህዝብ ተወካዮችን ያካተተ ነበር፡፡

የአማራና የትግራይ ክልል ጎንደር የተዘጋጀው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረክ ላይ ንግግሩ በስፋት ሲስተዋል የነበረው ፖለቲካው ላይ አተኩሮ ነው ፡፡ ይህም የሚያመለክተው በመድረኩ ላይ ፓርቲዎቹ ጥላቸውን እንዳጠሉበት ነው፡፡የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከተባለ ግን ለህዝቦች ነፃ እና ክፍት የሆነ መድረክ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ካህሳይ ገብረህይወት፣የረዳትፕሮፌሰር አበባውን ሀሳብ በማጠናከር ነው አስታያየት የሰጡት። የክልሎችን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ከተፈለገ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላቶቻቸውን በመያዝ ክልሎች ላይ ተገኝተው መወያየት ብቻ ሳይሆን ህዝቡን ሊወክሉ የሚችሉ ባለድርሻ አካላት ሊታከሉበት ይገባል። ጥናታዊ በሆነ መንገድ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ህብረተሰቡ ውስጥ ዘልቆ በመግባት ግንኙነት ማድረግ አለበት ይላሉ፡፡

እንደ መምህር ካህሳይ ማብራሪያ በክልሎች መካከል የተደረገው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የአገር ሽማግሌዎችን ያሳተፈ ቢሆንም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ባለድርሻ አካላትን አላካተተም ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡ይሄ በሥራ አስፈፃሚ የበላይነት የተካሄደ ነው፡፡እንዲህ ዓይነቱ መድረክ የፓርቲዎችን ግንኙነት ከማጠናከር በዘለለ ህብረተሰቡ ላይ ብዙም መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፡፡ፋይዳውም ከመገናኛ ብዙሀን ፍጆታነት የዘለለና ውኃ የሚያነሳ ነገር አይደለም ብለዋል፡፡

«የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ በትክክል መደረግ ካለበት የውይይት መድረኩ ከፓርቲዎች በዘለለ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ አድማሱን ማስፋት ያስፈልጋል፡፡መድረኩ ከፍተኛ የትምርት ተቋማትን፣ የወጣቶች ፎረምን ፣ሲቪክ ማህበራትንና የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችን ማካተት ይገባዋል » ሲሉ ነው የተናገሩት ፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር አበባው እንዳሉት ኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን መተግበር ከጀመረች አንስቶ ሁሉም ክልሎች በአንድነት ሳይሆን በተናጥል፤የኢትዮጵያ አንድነት ከማለት ይልቅ ክልልን ብቻ ማሰብ ጀምረዋል ፡፡ልማት፣ባህል ፣ ቋንቋ ፣ ትምህርት የሚለው ጉዳይ ሲነሳ በአብዛኛው ክልሉ ላይ ከማተኮር በዘለለ ኢትዮጵያ ወደ ሚለው አስተሳሰብ አልመጣም፡፡ህዝቡን ሲያስተሳስር የነበረው የማህበራዊ፣የኢኮኖሚ እና የባህል ግንኙነቶች ተረስተው ቆይተዋል፡፡ የፖለቲካ መድረኩ ግን ሁሉንም ክልሎች ያገናኛል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ፓርቲዎች በአንድ ጥላ ሥር ስላሉ ፡፡ነገር ግን የክልል ህዝቦችን እስካሁን ያገናኘ መድረክ ተፈጥሮ አያውቅም፡፡ በዚህ በኩል ሲታይ አሁን የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አዲስ እርምጃ ነው፡፡ ሆኖም ግን ግንኙነቱን በአመራሩ ብቻ መፈጠር የለበትም ፡፡

ለምሳሌ ክልሎች የባህል ልውውጥ ሲያደርጉ ፓርቲዎች ሳይሆኑ መድረኩን ማዘጋጀት ያለባቸው የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የባህል ማዕከል፣የኪነት ቡድኖች፣የሥነጥበብ ባለሙያዎች ስላላቸው በነሱ በኩል መሆን አለበት፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸውን ሚና መጫወት ይገባቸዋል፡፡እነዚህ አካላት የራሳቸውን ሚና መወጣት ሲችሉ ህዝብን ከህዝብ ማስተሳሰር፣ የባህል ልውውጥ ማድረግ ይቻላል፡፡በመሆኑም ለነዚህ ተቋማት ሀላፊነት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ መድረኩ ነፃ ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ድባብ አያጠላበትም፡፡ ህዝቡም በነፃነት ይናገራል፡፡

የፌዴራል አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ዘላቂ መፍትሄ ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ሲሳይ መለሰ፣ የክልሎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ህገመንግሥቱ በግልጽ የሚያስቀምጠው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች አንድ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት በገቡት ቃልኪዳን መሰረት በአገር ውስጥ ህብረ ብሄራዊነትን የመገንባት ጉዳይ ወሳኝ በመሆኑና ይሄንኑ ጉዳይ ለማጠናክር እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ ፡፡

አቶ ሲሳይ እንደሚሉት የፌዴራል መንግሥት የራሱ የስልጣን ወሰን አለው፡፡ ክልሎችም የየራሳቸው ስልጣን ወሰን አላቸው፡፡የክልሎች የራስ አስተዳደርና የጋራ አስተዳደር አለ፡፡የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ የጋራ አስተዳደርን ከማጎልበት የፌዴራል እና የክልል እንዲሁም የክልልና የክልል ግንኙነት እየተጠናከረ እንዲሄድ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፡፡ የእርስ በእርስ ግንኙነቱ እየተጠናከረ በሄደ ቁጥር ደግሞ ብሄራዊ አንድነት እንዲጎለብት ያግዛል ፡፡

በኦሮሚያ እና አማራ፣ በትግራይና በአማራ ክልል የተደረጉ ግንኙነቶች ህዝቦች የጋራ አንድነታቸውን ሊያጠናክር እና የህብረ ብሄር ሥርዓት አካል መሆናቸውን ሊያጎለብት የሚችል የተለያዩ መድረኮችን ማድረጋቸው በህዝቦች መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር የራሱ የሆነ ጠቀሜታ አለው ፡፡

‹‹የፌዴራል ሥርዓቱን የሚፈታተኑ በተለያየ ጊዜ በመንግሥት የሚገለፁ አስተሳሰቦች አሉ፡፡ እነዚህም የመልካም አስተዳደርን ችግሮችን ጨምሮ የጥበት እና የትምክት ብሎም ለራስ ብቻ የማድላት አስተሳሰብ ናቸው፡፡እነዚህ አመለካከቶች የመላው ህዝብ ሳይሆኑ በጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች የሚስተዋል ነው ፡፡በመሆኑም እንደእነዚህ ዓይነት አስተሳሰቦችን እየሰበሩ የህዝቦችን ግንኙነት ማጠናከር አስፈላጊ በመሆኑ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረኮችን ማዘጋጀት አስፈልጓል›› ብለዋል ፡፡

‹‹በህዝቦች መካከል ቀድሞም ቢሆን ልዩነት የለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያየ መንገድ የተሳሰረ ነው›› የሚሉት አቶ ሲሳይ አሁን እየተዘጋጁ ያሉ መድረኮችም የነበረውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንጂ አዲስ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ዋናውና ቁምነገሩ ግንኙነትን የበለጠ ማጎልበት ነው፡፡ በመሆኑም በክልሎች መካከል የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡

ከዚህ ቀደም የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስተዳደራዊ ወሰን ሲካለል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ በርካታ ኮንፈረንሶች መካሄዳቸውን አቶ ሲሳይ ያስታውሳሉ። በግንኙነቶቹም በክልሎች መካከል ሲነሱ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት የጋራ አስተሳሰብ ላይ ተደርሷል፡፡በትግራይና በአማራ ክልል መካከል ከዚህ ቀደም ከአስተዳደራዊ ወሰን ማካለል ጋር ተያይዞም አለመግባባቶች የነበሩ ቢሆንም ችግሮቹን ለመፍታት በተደረጉ ኮንፈረንሶች፣አለመግባባቶች ተፈተዋል፡፡ከዚህ በኋላ ግን የበለጠ የህዝብ አንድነትን ለማጎልበት ውይይቶችን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

በርካታ የአማራ ክልል ተወላጆች በኦሮሚያ ክልል ይኖራሉ፡፡በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ማህበረሰብ በአማራ ክልል ውስጥ ይኖራሉ፡፡እነዚህን አንድ ላይ ተሳስረው በኖሩ ህዝቦች መካከል አንድ አንድ አካላት የሚፈጥሯቸውን አለመግባባቶችን ለመፍታት በመካከላቸው የበለጠ ግንኙነቱ እንዲጠናከር የሚያግዝ ነው።

እንደ አቶ ሲሳይ ማብራሪያ በክልሎች መካከል የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በህዝቦች መካከል መተሳሰብ እየጎለበተ እንዲሄድ ፣መከባበር እንዲኖር ይረዳል፡፡ተደጋግፎ ማደግን ያጎለብታል፡፡የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦች በአገሪቱ የትኛውም አካባቢ የመኖር የመስራትና ሀብት ንብረት የማፍራት መብት አላቸው፡፡ይሄ መብታቸው በህገ መንግስቱ አንቀጽ 40 ላይ በግልጽ የተቀመጠ ነው። ሁሉም ሰው ሊያከብረውና ሊተገብረው የሚገባ። የብሄር ብሄረሰቦች መብቶችን እና የዴሞክራሲ እሴቶችን እያጎለበቱ እንዲሄዱ ያደርጋል፡፡ ይህም ለዴሞክራሲ ባህል መጎልበት የራሱ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ በህገ መንግስቱ የተቀመጡ የግለሰብ እና የቡድን መብት ሳይነጣጠሉ እንዲከበሩ ይረዳል፡፡

በህዝቦች መካከል መከባበር፣መቻቻልና መደጋገፉ እየተጠናከረ በሄደ ቁጥር ሰላም እየጎለበተ ይሄዳል፡፡በአገሪቱ ሰላም እየጎለበተ በመጣ ቁጥር ለልማት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡የውጪ ባለሀብቶችን ወደ አገር ውስጥ ለመሳብ ያስችላል፡፡መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የራሱ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡በአጠቃላይ ለባህል ልውውጥ፣ለዴሞክራሲ፣ለኢኮኖሚና ለማህበራዊ እድገት የህዝቡን ግንኙነት ማጠናከር ወሳኝ ነው፡፡

አቶ ሲሳይ እንዳሉት የመልካም አስተዳደርን ችግር መፍታት የመንግሥት ሚና ብቻ አይደለም፡፡በወረቀት ላይ የተቀመጠ ሲስተም በመዘርጋት ብቻ ችግርን መፍታት አይቻልም፡፡ስለዚህ በመልካም አስተዳደር ሥራ ላይ ህዝብም መሳተፍ መቻል አለበት፡፡አስተሳሰቡ አብሮ ማደግ አለበት፡፡በየደረጃው የሚገኝ የህብረተሰብ ክፍል የራሱን ሚና ማሳረፍ ይጠበቅበታል፡፡

ይሄን የመልካም አስተዳደር ችግር የወለዳቸውን ግጭቶች ለማርገብም ሆነ ለመድፈቅ ያግዛል።በህዝቦች መካከል የሚፈጠሩ አሉባልታዎችና ጥርጣሬዎች እንዳይኖሩ ያደርጋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር አበባው እንደሚሉት የኢትዮጵያ ህዝቦች ለብዙ ዘመናት አንድ ላይ የኖሩ፣ ትልቅ መስተጋብር ያላቸው ናቸው፡፡በመሆኑም በህዝቦች መካከል ግጭት ሲፈጠር የግጭቱ መንስኤ ምንድነው ብሎ መለየት ያስፈልጋል፡፡ግጭቱ በማን ተፈጠረ፣ ለምን ተፈጠረ፣ አጥፊው ማን ነው ብሎ መለየት ያስፈልጋል፡፡እስካሁን በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቆም የሚወሰዱ የፖለቲካ እርምጃዎች የግጭቱን ምንጭ ከስር መሰረቱ እያደረቁ አይደለም፡፡መንግሥት የቅጣት እንጂ የመፍትሄ እርምጃ እስካሁን ሲወስድ ታይቶ አይታወቅም፡፡ ግጭቱን ለመፍታት ለህዝብ ወይም ለአገር ሽማግሌ እድል ቢሰጥ ኖሮ ችግሩን ከሥር መሰረቱ ሊያደርቁት ይችሉ ነበር።

መምህር ካሳይ የፕሮፌሰር አበባውን ሀሳብ ይጋራሉ። በአገሪቱ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን ከህዝቦች ጋር ተነጋግሮ መፍታት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው ይናገራሉ ፡፡በእሳቸው እምነት ያለውን ችግር ፈትቶ የህዝብ አንድነትን ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር ቁጭ ብሎ ጥናት ላይ ተመስርቶ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የአገር አንድነት የሚባለው ህዝቡ ነው፡፡መነጋገር የሚያስፈልገውም በፖለቲካ ፓርቲ አባላት ብቻ ሳይሆን ህዝብ ውስጥ ተገብቶ ነው፡፡አመራር ላይ የተቀመጡ የመንግሥት አካላትም ቅንነት በተሞላበት መንገድ ስልጣናቸውን በተግባር ላይ ማዋል አለባቸው፡፡ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ፉክክር ትተው ቀና በሆነ መንገድ ህዝብን በሚጠቅም መልኩ በአገሪቱ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን በቁርጠኝነት ለመፍታት መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ይህን ማድረግ ከተቻለ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ፡፡ የህዝብ ለህዝቡም ግንኙነት ፍሬ ያፈራል።

አቶ ሲሳይ በበኩላቸው በቀጣይ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል የመንግስታት ግንኙነት መጠናከር አለበት፡፡ይህም የፌዴራል መንግሥት ከክልሎች፣ ክልሎች ከከልሎች ጋር የሚያገናኝ ነው፡፡

የክልሎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ በጣም መጠናከር አለበት፡ አጎራባች ክልሎችን በልማት የማስተሳሰር ሥራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ይሄም በክልሎች መካከል የሚኖረውን የልማት ክፍተት ሊሞላ የሚችል ነው፡፡ የሁለቱን ክልል ማህበረሰቦች በጋራ ሊጠቅም የሚችል የልማት መስኮችን በመለየትና በማሳየት ተከታታይነት ባለው መልኩ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የህገመንግሥት አስተምሮን በሥፋት በየደረጃው ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ማስረፅ በቀጣይ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ወጣቱ ላይ ኢትዮጵያዊነት ማለት ምን እንደሆነ በሚገባ እንዲረዳ በትምህርት ቤት ደረጃ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡

አቶ ሲሳይም የመፍትሄ ሀሳብ በማለት የጠቀሱት እንደ አገር ችግሮች ሲከሰቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ፈጣን ምላሽ ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡ በአገሪቱ ለሚከሰቱ እያንዳንዱ የግጭት ምክንያቶች እየለዩ ፈጣን ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡በመሆኑም ሁሉም የክልልና የፌዴራል አካላት ተቀናጅተው መስራት አለባቸው፡፡ ይህም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የበለጠ እየተጠናከረ እንዲመጣ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር አበባው በቀጣይም የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎና የአገር ሽማግሌዎችን ሚና ማሳደግ ሊሠራ የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

 

ሰብስቤ ኃይሉ

 

 

 

Published in ፖለቲካ
Saturday, 02 December 2017 17:51

ከቴክኖሎጂ ሽግግሩ ...

 

ቴክኖሎጂን መቅዳት፣ማላመድና መፍጠር እንዲሁም ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማኅበረሰቡ ማድረስ የአገር ኢኮኖሚን ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ኢትዮጵያ አዳዲስ ቴክኖሎጂ ፈጣሪና ተጠቃሚ ከሆኑ አገራት በመቅዳት በማላመድ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ብትጀምርም ገና ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባት በዘርፉ የተሰማሩ ተዋንያን ይናገራሉ፡፡በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እድገት ውስጥ ካለው ፋይዳ አንፃርም በቀጣይ በአገሪቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግና አገር በቀል ቴክኖሎጂን ማሳደግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት አለበት ሲሉ ይመክራሉ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ኢንጅነር ክብሮም ኃይሉ፣የቴክኖሎጂ ሽግግር በአንድ አገር ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት የሚያመጣ መሆኑን ይናገራሉ፡፡የቴክኖሎጂ ሽግግር ከአገራት እድገት ጋር በቀጥታ ተያያዢነት አለው፡፡ ምክንያቱም የእድገት መሰረቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር ነው፡፡በአለም ላይ አደጉ የሚባሉ አገራት የብልፅግናቸው ቁልፍ ሚስጥር ቴክኖሎጂ ላይ መስራታቸው ነው።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂ ሽግግር የማድረግ አቅሟ ጅምር ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚናገሩት ኢንጅነር ክብሮም አገሪቱ ከውጪ ወደ አገር ውስጥ እያደረገች ያለው የቴክኖሎጂ ሽግግርና የማላመድ አቅም በቁጥር ለመግለፅ ጥናት እንደሚያስፈልገው ይገልፃሉ፡፡

ሆኖም ግን ዛሬ አገሪቱ እየተጠቀመችበት ያለው ቴክኖሎጂ እአአ በ1930ዎቹ አካባቢ አሜሪካ እና አውሮፓ ሲጠቀሙበት የነበረ ነው ፡፡ ይህም በአገሪቱ እንደ ትልቅ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚቆጠርበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ይህም የሚያመለክተው ቴክኖሎጂን የመቀበል አቅማችን በጅምር ደረጃ እንዳለና በቀጣይ ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ ነው፡፡

እንደ ኢንጅነር ክብሮም ገለፃ በአገሪቱ ቴክኖሎጂን በሥፋት ለማምጣት በዋናነት ዘርፉን የሚመሩ አካላት ከቴክኖሎጂው ጋር ቅርብ ቁርኝነት ያላቸው መሆን ይገባቸዋል፡፡በአገሪቱም ቴክኖሎጂ መር የኢኮኖሚ እድገት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ከሁሉ አስቀድሞ ህብረተሰቡ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለአገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ጠቀሜታ አለው የሚለውን ማመንና ማስረጽ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በአገር ደረጃ ቴክኖሎጂዎችን የሚመራ ተቋም መፍጠር ይገባል፡፡ በዚህም የሚሳተፉ የግል ኢንተርፕራይዝ እንዲኖር ማበረታታት እና ይህንንም መሰረት ያደረገ የምርምር ተቋም መገንባት ቁልፍ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡

‹‹በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ዘርፍ በአለም ላይ ከፍተኛ የሆነ ቴክኖሎጂ አለ›› የሚሉት ኢንጅነር ክብሮም ቴክኖሎጂው‹‹ኦፕናይቲ ማኔጅመንት ሲስተም›› ይባላል፡፡ ይህም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚታየውን የመልካም አስተዳደር፣ የማኔጅመንት እና ሌሎች ችግሮችን ለማስቀረት ዓይነተኛ መፍትሄ ነው ፡፡

የአሜሪካና አውሮፓ አገራት ኩባንያዎች ይህን ቴክኖሎጂ በመጠቀማቸው በዓመት ያላአግባብ የሚወጣን 1ነጥብ 8ቢሊዮን ዶላር ማዳን ችለዋል፡፡በመሆኑም ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪን የሚመራ አካል ‹‹ኦፕናይቲ ማኔጅመንት ሲስተም›› ቴክኖሎጂን በአገር ውስጥ ማላመድ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ቴክኖሎጂው በተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሰራር እንዲኖርና ግንባታዎች በተያዘላቸው በጀት፣ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቁ ይረዳል፡፡ሆኖም ግን ወደተግባር ለመቀየር የሁሉም አካል ቀና አስተሳሰብና አመለካከት ሊታከልበት ይገባል፡ ይላሉ።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አርጋው አሻ ኢንስትቲዩት ከተቋቋመበት ከ2006 .ም መጨረሻ ጀምሮ በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ መቆየቱን ይናገራሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት «ጂኦ ሴንቴቲክ» የሚባል ቴክኖሎጂ ወደ አገር ውስጥ አምጥቶ እንዲላመድ አድርጓል፡፡ ቴክኖሎጂው የመንገድ መሰነጣጠቅን ማስቀረት የሚያስችል ነው፡፡ መንገድ እስከ 40 ዓመት ካለጥገና እንዲቆይ ያግዛል፡፡እንዲሁም ከባቡር መስመር ዝርጋታ ጋር ተያይዞ የመጡ እንዲሁም ህንፃዎች ወደ ጎን ሳይሆን ወደ ላይ እንዲያድጉ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎች ወደ አገር ውስጥ መግባቱን ይጠቅሳሉ፡፡

እንደ ዶክተሩ ማብራሪያ የአገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እድገት ከቴክኖሎጂ አንፃር ሲታይ በአራት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ይህም ከ1968 .ም በፊት አብዛኛዎቹ በአገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ላይ ሲሳተፉ የነበሩት የውጪ ኩባንያዎች በመሆናቸው ትልልቅ የመንገድና የህንፃ ሥራዎች ቢሰሩም የቴክኖሎጂ ሽግግር አልነበረም፡፡

1968 ወዲህ ደግሞ የግል ኮንትራክተሮች ብቅብቅ ያሉበት ወቅት በመሆኑ በህንፃ ግንባታው ዘርፍ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ከውጪ የማምጣት ሁኔታ ነበር። ሆኖም ግን ብዙ ሳያድግ ከስሟል፡፡

1991 .ም አካባቢ ዘርፉ የግል አማካሪዎችና ኮንትራከተሮችን እያበረታታ በመምጣቱ የሪል እስቴት ግንባታዎች እያደጉ መጥተዋል፡፡በዚህም 1400 የሚሆኑ ሪል እስቴቶች ፍቃድ ወስደው 100 የሚሆኑ የውጪ ኩባንያዎች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ከህንፃ ጋር ተያይዞ የቴክኖሎጂ ሽግግር ተደርጓል፡፡

1997.ም ጀምሮ መንግሥት በቤት ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ‹‹ፕሪካስት›› በር እና መስኮት የሚሰራባቸውንና ሌሎች አለማት የሚጠቀሙበትን ቴክኖሎጂ ማምጣት ተችሏል፡፡ይህም በተለይ በህንፃ ግንባታው ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት መኖሩን ያሳያል፡፡በአጠቃላይ በአገሪቱ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ሽግግሩ በጅምር ላይ ያለና እያደገ የመጣ ነው፡፡

‹‹ቴክኖሎጂን በሁለት መንገድ ማምጣት መጠቀም ይቻላል›› የሚሉት ዶክተር አርጋው አንደኛ አዲስ ነገር በመፍጠር ሲሆን ሁለተኛው ሌሎች የሰሩበትን ቴክኖሎጂ ከአገሩ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ በማላመድ የማስፋፋት ሥራ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት አዲስ ቴክኖሎጂ መፍጠር ሳይሆን ሌሎች አገር ላይ የተሰሩ ለረጅም ዓመት የተጠቀሟቸውን ቴክኖሎጂዎች ወደ አገር ውስጥ አስገብቶ ማላመድ፣ ማስፋፋትና ማስተላለፍ ነው፡፡ ምክንያቱም ከሌሎች አገራት ቴክኖሎጂዎች ሲመጡ ለሠራው ሰው የፈጠራ ሥራ ባለቤትነት ይሰጣል ፡፡ሁለተኛ ደግሞ ቴክኖሎጂው ሲሰራ እስታንዳርዱን ጠብቆ ተፈተሾ ነው፡፡የኢትዮጵያ የህንጻ ኮዶችም የተወሰዱት አብዛኛዎቹ ከአውሮፓ በመሆኑም አውሮፓ አገር ውስጥ የተሰራን ቴክኖሎጂ ወደ እኛ አገር ማላመድ አይከብድም፡፡የተወሰነ የአየር ጸባይን በማስተካከል ወደ አገር ውስጥ ማምጣት እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡

በአገሪቱ ጥሩ የሚባሉ አገር በቀል ቴክኖሎጂዎች መፈጠሩን የሚናገሩት ምክትልዋና ዳይሬክተሩ ይህም የብሎኬት ብክነት የሚያስቀር፣ግንባታ እንዲፋጣን የሚያደርግና ብሎኬት ሲደረደር ሲሚንቶ ሊቀመጥበት የሚችል ቴክኖሎጂ በግለሰብ ደረጃ ተሰርቷል፡፡ሥራውም ባለፈው አመት ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ባለቤቶች እንዲተዋወቅ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም የብረት አቆራረጡ ምን መምሰል አለበት የሚለውና ብረት በትንሽ ማሽኖች የሚቆረጥበት ቴክኖሎጂ በአገር ውስጥ ተሰርቷል ፡፡

አገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የውጪ ምንዛሬ ወጪን እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ሥራ በፍጥነት እንዲሰራና ብክነት እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ ሆኖም ግን አገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን በማሳደግና በመጠቀም በኩል መንግስት ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከሰጠው ትልቅ ትኩረት አንጻር ጅምር ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

በዘርፉ የሚስተዋለው ችግር በማለት ዶክተር አርጋው የጠቀሱት ህብረተሰቡ አገር ውስጥ በሚፈጠር ቴክኖሎጂ ላይ እምነት ማጣት፣አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን አለመቀበል፣የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር በሥፋት አለመኖር፣ቴክኖሎጂዎችን ወደ ታች አለማውረድ እንዲሁም አዲስ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ባይስፋፋ የሚል አመለካከት መኖሩ እና በመገናኛ ብዙኃን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በበቂ ሁኔታ አለማስተዋወቅ ናቸው።

እንዲሁም ቴክኖሎጂዎች በየቦታው የሚሰፋፉበትን በጀት መንግስት የመደበባቸው መስሪያ ቤቶች ያሉ ቢሆንም ያልመደበባቸውም መሥሪያ ቤቶች መኖራቸው ቴክኖሎጂዎችን በስፋት እንዳይስፋፋ ማነቆ መሆናቸውን ዶክተሩ አስረድተዋል፡፡

በቀጣይ በአገሪቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ቴክኖሎጂ ይዘው የሚመጡ የውጪ ኩባንያዎችን ማበረታታት፣የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ከውጪዎች ጋር እንዲላመዱና ተጣምረው እንዲሰሩ ማድረግ፣ ቴክኖሎጂን ለመቅዳትና ለማላመድ ሰዎችን በውጪው አላም ማሰልጠን እና ትልልቅ የሀይል ማመንጫ ግድቦች ሲገነቡ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ከውጪዎቹ ጋር አብረው እንዲሰሩ ማድረግ፣ ያስፈልጋል ሲሉ የመፍትሄ ሀሳብ ጠቁመዋል።

 

ሰብስቤ ኃይሉ

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ሰሜን ኮሪያ አዲስና ስኬታማ ነው ያለችውን አህጉር ተሻጋሪ ባሊስቲክ ሚሳይል ከቀናት በፊት ተኩሳለች። ይህ ሚሳይል ሃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ የአሜሪካን ሁሉንም ክልሎች ሊመታ እንደሚችል የፒዮንግያንግ መንግስት የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግሯል። ሰሜን ኮሪያ እስከዛሬ ከተኮሰቻቸው ሚሳይሎች በሙሉ ረጅም ርቀት በመጓዝ ወደር እንደሌለውም ገልጿል። ደቡብ ኮሪያም ለባላንጣዋ ሰሜን ኮሪያ መልስ ይሆን ዘንድ ሁለት ባሊስቲክ ሚሳይሎችን ተኩሳለች። ሚሳይሉ አራት ሺ አራት መቶ ሰባ አምስት ኪሎ ሜትር ከፍታ ሃምሳ ሦስት ደቂቃ ፈጅቶ ዘጠኝ መቶ ሃምሳ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዟል። ከጃፓን ሰሜናዊ የባህር ዳርቻ ሁለት መቶ ሃምሳ ሜትር ርቀት ላይም አርፏል። የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ኬ ሲ ኤን ኤ በተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው «አሁን በታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣት የኒውኩሌር ባለቤት አገር ፈጥረናል» ሲሉ ለአሜሪካ ማስፈራሪያ የሚመስል መልዕክት አስተላልፈዋል።

በጉዳዩ ላይ ጥናት የሚያካሂደው የአሜሪካ ሳይንቲስቶች ህብረት እንደተናገረው አዲሱ ሚሳይል አስራ ሦስት ሺ ኪሎ ሜትር የመጓዝ አቅም ስላለው የትኛውም የአሜሪካ ግዛት ይደርሳል። ነገር ግን የኒውኩሌር አረር ተሸክሞ አሜሪካ መድረስ እንደማይቻለው ህብረቱ አስረድቷል። ሰሜን ኮሪያ ግን ሂው ሶንግ 55 ኒውኩሌር ተሸክሞ አሜሪካ የመድረስ አቅም እንዳለው አስረግጣ ተናግራለች።

ባለሙያዎች እንደሚናገሩት አህጉር ተሻጋሪው ባሊስቲክ ሚሳዔል አሜሪካ መድረስ አይችልም። ሰሜን ኮሪያ በምትለው ደረጃ ሚሳዔሎቿ ሊደርሱ የሚችሉት አሁን ካሉበት በሁለትና ሦስት እጥፍ ጊዜ ይፈጅባቸዋል ሲሉም ያብራራሉ።

የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ጀምስ ማቲስ ሰሜን ኮሪያ አሁን የተኮሰችው ሚሳዔል ከዚህ በፊት ከተኮሰቻቸው ሚሳዔሎች ከፍ ብሎ እንደተምዘገዘገና ይህም ሙከራ ዓለም አቀፍ ትንኮሳ እንደሆነ ተናግረዋል። የሰሜን ኮሪያው ሚሳዔል ተተኩሶ አየር ላይ እንዳለ ማብራሪያ የተሰጣቸው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጉዳዩ መላ እንደማያጡ በአገራቸው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲኤን ኤን ቀርበው ተናግረዋል። ይህም ሰሜን ኮሪያ እልህ ውስጥ ገብታ እንዳትተኩሰውና የብዙዎች ስጋት እየሆነ የመጣው የዓለም ጦርነት መነሻ እንዳይሆን በብዙዎች ዘንድ ስጋት ፈጥሯል።

በሃዋይ ፓሲፊክ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርና የቀድሞ የአሜሪካ ፓሲፊስ ኮማንድ ጥምር የስለላ ማዕከል ዳይሬከተር የነበሩት ካርል ስቹዉስለር ሰሜን ኮሪያና ደቡብ ኮሪያ በሚሳዔል ዘርፉ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ይናገራሉ። ከወራት በፊት ሰሜን ኮሪያ አራት ሚሳኤሎችን ወደ ጃፓን ባህር በማስወንጨፍ ቶኪዮን መተንኮሷ ይታወሳል። በዚያን ወቅት ኪም ጆንግ ኡን እንዲተኮስ ካዘዙት አራት ሚሳኤሎች መካከል ሦስቱ ከጃፓን የባህር ዳርቻዎች ከሦስት መቶ ኪሎ ሜትር ባነሰ ስፍራ ርቀት ላይ ወድቀዋል። ከሰሜን ኮሪያ ቾንግ ቻንግ የተተኮሱት ሚሳኤሎች አንድ ሺ ኪሎ ሜትር ተጉዘው የጃፓን የባህር አጥር ላይ አርፈዋል። ይህ የሚሳኤል ክንዴን እዩልኝ ተኩስ በደረቅ ጠጣር ነዳጅ ከመወንጨፉ በፊት የሚቀጣጠለውን «ቦክሶንግ የተባለውን ሚሳኤል ካስወነጨፈች ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው አራቱን ሚሳኤል የተኮሰችው። በዚህም ሳታበቃ ከአምስት ወር በፊት አንድ ሺ ኪሎ ሜትር ተጉዞ የጃፓን አየር መከላከያ ቀጣና ውስጥ የዘለቀ ሦስት ሚሳኤሎችን አስወንጭፋለች። ይህ ማለት ሰሜን ኮሪያ በትጋት ሚሳኤሎችን ታመርታለች ማለት እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ። ስለዚህ ድንገት ወደ ጦርነት ቢገባ የሚቀመጥ አለ ማለት ነው። ይህም ከዚህ በፊት ከነበራት የበለጠ ሚሳዔል ባለቤት ናት በማለት የተከታታዩን ተኩስ ሚስጥር ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ። ሰሜን ኮሪያዎቹ በብዛት ማምረት ብቻ ሳይሆን የሚሳኤል ቴክኖሊጂያቸው መበልፀጉም በአሁኑ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳዔል አስመስክረዋል።

ከዚህ ቀደም በሚድል ቤሪ የዓለማቀፍ ጥናት ማዕከል ፕሮፌሰር የሆኑት ጄፍሪ ሉዊስ ለሲኤን ኤን እንደተናገሩት ሰሜን ኮሪያ ከዚህ በኋላ የሚሳዔል ሙከራ አታደርግም ብለው ነበር። ምክንያታቸውም የከዚህ ቀደሙ ተኩስ የሚሳኤል ማስወንጨፊያቸውን በርከት ያሉ ሚሳኤሎችን በአንድ ጊዜ የማስወንጨፍ አቅም ለመፈተን ያደረጉት ሙከራ ነው። ይህም ወታደራዊ አቅማቸውን በኒውኩሌር ለማዘመን የሚያልሙ አገራት ባህሪ ነው። በዚህም ሰሜን ኮሪያ ያሳየችው ትልቅ ለውጥ እንደሆነ ይታመናል። ሰሜን ኮሪያ ባለፈው የፈረንጆቹ መስከረም የሰማት የለም እንጂ ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን የሚስተካከሉ የኒውኩሌር መሳሪያዎች በእጇ እንደሆኑ ተናግራለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምታደርጋቸው የሚሳዔል ተኩሶች የአሜሪካ የሆነው የደቡብ ኮሪያዎቹን የኒውኩሌር ሚሳኤል መከላከያ አቅም ለመፈተን እንደተተኮሰ የሚያምኑም አልጠፉም። አንድ የሚሳኤል መከላከያ አንድ የሚሳኤል ተኩስን ማቆም ይቻለው ይሆናል። አራት በአንድ ጊዜ ማቆም ግን እንደማይቻለው ፕሮፌሰር ሉዊስ ይናገራሉ። ለዚህም ነው ሰሜን ኮሪያ አራት ሚሳኤል አንድ ላይ በመተኮስ የባላንጣዋ ደቡብ ኮሪያን የመከላከል አቅም ለመፈተሽ የፈለገችው ሲሉም የሚናገሩት።

አንዳንድ ተንታኞች እንደሚያስረዱት የአሁኑ ተኩስ ሰሜን ኮሪያ ትዕግስቷ እንዳለቀና የአሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ጥምረት እንዳላማራት በማስረዳት ወደ ኒውኩሌሩ ዱላ እንደምትገባ ያላትን ፍላጎት ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል። ቻይና የሰሜን ኮሪያ ጥብቅና ቅርብ ወዳች መሆኗ ይታወቃል። የቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ ዓመታዊ ስብሰባ በተለምዶው ብሔራዊ የህዝብ ኮንግረንስ ስብሰባ በመዲናዋ ቤጂንግ ከወራት በፊት ተካሂዷል። የሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ተኩስ ለቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ ስብሰባ በደስታ መግለጫነት የቀረበ ሳይሆን ቻይና የሰሜን ኮሪያን የድንጋይ ከሰል ሙሉ በሙሉ በዘንድሮው ዓመት አልሸምትም ማለቷን ተከትሎና፤ በቻይና እንክብካቤ የታጀበ ነው የሚባለው የሰሜን ኮሪያው ፕሬዚዳንት ኪምጆንግ ሁን ወንድም ኪምጆንግ ናም ሞት ጀርባ ሰሜን ኮሪያ ብትክድም እጇ አለበት ብላ ቻይና በማመኗ ነው።

የሰሜን ኮሪያን የሚሳኤል ሙከራ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ «አዲሱ ወረራ» ሲሉት፤ የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ባለስልጣናት ሚሳኤሉ የተተኮሰበትን ቴክኖሎጂ ምርመራ ላይ ናቸው ሲል ቢቢሲ በዘገባው አስፍሮታል። የአሜሪካ መንግስት የወጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ማርክ ክላተንበርግ ሰሜን ኮሪያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የረቀቀውና ምንም አይነት የባሊስቲክ ሚሳኤል ሙከራ እንዳታደርግ የሚያግዳትን ክልክላ ጥሳ ያደረገችው ሙከራ እጅግ የተሳሳተ እንደሆነ ሲገለፅ ቆይቷል።

የአሜሪካ መከላከያ በበኩሉ የሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራ ቴክኖሎጂ ለአሜሪካ ስጋት እንደማይሆን በተደጋጋሚ ሲገልፅ ይሰማል። የቻይና ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ሰሜን ኮሪያ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የሚሳኤል ሙከራ እንዳታደርግ ያገዳት ቢሆንም ህጉን ጥሳ ሙከራ ማድረጓ ተገቢ እንዳልሆነ ከዚህ ቀደም ሲገልፅ ነበር። እንደ ሰሜን ኮሪያ ባላንጣዋ ደቡብ ኮሪያ ሚሳኤሎችን በመተኮስ ያላትን አቅም ባታሳይም የሚሳኤሉን ቴክኖሎጂ ደረጃ መረጃ ላቀበላት ስምንት መቶ ስልሳ ሺ ዶላር ለመክፈል ፍላጎት እንዳላት ለሰሜን ኮሪያዎቹ የቴከኖሎጂው ባለቤቶች ጥሪዋን ማስተላለፏ አይዘነጋም።

 

ቦጋለ አበበ

 

 

Published in ዓለም አቀፍ

 

በአፋር ብሔረሰብ የማህበራዊ ትስስር መገለጫ የሆኑ በርካታ ባህላዊ እሴቶች አሉ። ከነዚህ አንዱ «ኦንኦር» የሚባለው ሥርዓት ነው። ይህ ባህላዊ ሥርዓት በአፋር ብሔረሰብ ልጅ ሲወለድ ቤተሰቦቹ ለልጁ ያላቸውን ምኞት ወይም ልጁ ሲያድግ እንዲሆንላቸው የሚፈልጉት የወደፊት እሱነት የሚገልጹበት ሥርዓት ነው። በዚህ ባህላዊ ሥርዓት ከልጁ ወላጅ እናት ዘመዶች መካከል አንዱ ተመርጦ ህፃኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ውሃ፣ ቴምር፣ ወተት ወይም ሌላ የሚበላ ነገር እንዲቀምስ ይደረጋል። በዚህም ልጁ ወደፊት ቤተሰቦቹ የተመኙለትን እንዲሆን በኦንኦር ሥርዓት ሙሉ እምነት አላቸው። ልጁን ለመጀመሪያ ጊዜ ምግብ ወይም ውሃ በማቅመስ ኦን ኦር ካደረገው ቤተሰብ ጋርም የጠበቀ ማህበራዊ ግንኙነት እንዲፈጠር በማድረግ ይህ ባህላዊ ሥርዓት ማህበረሰባዊ ወዳጅነትን የበለጠ ያጠናክራል።

በአፋር ማህበራዊና ባህላዊ ሥርዓት ውስጥ «ፍራንጋኢና» የሚባል እሴት አለ። ይህም በቤተሰባዊ ህይወት ዙሪያ ልጆችን ከሌላ ቤተሰብ ልጆች ጋር በመቀላቀል ወዳጅነት በመፍጠር ቤተሰባዊ ትስስር የሚጠናከርበት ነው። ይህ ባህላዊ ሥርዓት «ልጄ የልጅህ ወዳጅ ነው» በሚል የሚገለጽበት ሁኔታም ልጁን በሚፈለገው ሰው ትከሻ ወይም እጅ ላይ በማስቀመጥ የሚከናወን ነው። በዚህ ሥርዓት ልጆቻቸው ወዳጅ እንዲሆኑ በፈለጉ ቤተሰቦች መካከል መልካም ግንኙነት ይፈጠራል። የልጆቹን እድገት ተከትሎ እርስ በርስ የሚገናኙበትና በልጅነት የተፈጠረውን ትስስር ዘላቂነት እንዲኖረው ቤተሰባዊ ወዳጅነትን በማጐልበት ከፍተኛ ድርሻ ያለው ነው።

የአፋር ብሔረሰብ ህዝቦች «ኢብናይቲኖ» የሚባል ማህበራዊ ባህላዊ እሴት አላቸው። ይህም በአፋር ያለው እንግዳ ተቀባይነት በሚገባ የሚገለጽበት እሴት ነው። ኢብናይቲኖ ለእንግዳ የሚደረግ አቀባበል ነው። በዚህ መሠረት አንድ ሰው የትም ቢሆን ከቤቱ ወጥቶ ራቅ ወደአለ ቦታ ሲሄድ ቢርበኝና ቢጠማኝ ብሎ ስንቅ አይቋጥርም። ዝም ብሎ መሄድ ብቻ ነው። መንገድ ላይ ቢርበውና ቢጠማው ባገኘው ሰው ቤት ጎራ ብሎ በማረፍ መመገብ ይችላል። በሄደበት ሁሉ እንግዳው ተቀባይ አለው። በዚህ የተነሳ መንገደኛው ባረፈበትና በተስተናገደበት ቤት ካለው ቤተሰብ ጋር ግንኙነት በመፍጠር ወዳጅነት ይመሰረታል። ይህ ቤተሰባዊ ትስስር በአንድ ቀን ግንኙነት ተመስርቶ ዘላቂነት ያለው ነው።

የአፋር ብሔረሰብ ሌላው የማህበራዊ ባህላዊ መገለጫ «ሀራይ» የሚባለው እሴት ነው። ይህም በአፋር ያለውን የመተጋገዝና የመደጋገፍ ባህል የሚገልጽ ነው። በዚህ ባህላዊ እሴት ህዝቡ በደስታም ይሁን በሀዘን የሚያደርገውን የመተጋገዝ ባህል በመግለጽ ትስስሩን የሚያጠናክርበት ነው። በሀዘን ወቅት ብቻ ሳይሆን አቅም የሌለው ሰው ትዳር እንዲመሰርት እስከማድረስ ድረስ ድጋፍ ይደረግለታል። ግለሰቡ ትዳር እንዲመሰርት ብቻም ሳይሆን በቀጣይነት ራሱን እንዲችልም ግመል፣ ፍየል ወይም በግ ተዋጥቶ ይሰጠዋል። ከትዳር በዘለቀም ቤተሰባዊ ህይወቱን እንዲመራ ራሱን እንዲችል ይደረጋል።

በአፋር ብሔረሰብ ውስጥ ያለው «እድቦንታ» የተባለው ባህላዊ ሥርዓትም ችግር ያጋጠመው በተለይም የተፈጥሮም ይሁን ሰው ሠራሽ አደጋ የደረሰበትን ሰው መልሶ በማቋቋም ህብረተሰቡ የላቀ ተሳትፎ የሚያደርግበት እሴት ነው። ይህም በችግር ጊዜ ደራሽ መኖሩን የሚገልጽበት ሥርዓት ነው። «ከሀራይ» እና «ከእድቦንታ» ሥርዓቶች ጋር ተያያዥነት ያለው «ኩራ» የተባለው እሴት ሌላው የአፋር ብሔረሰብ ማህበራዊ ትስስር መገለጫ ነው። የኩራ ሥርዓት በሀዘን ወቀት በተለይም ሰው የሞተባቸውን ግለሰቦች ለማጽናናት እና ሀዘንን ለማረሳሳት የሚከናወን ባህላዊ ሥርዓት ነው። በዚህም ሀዘን ያጋጠመውን ቤተሰብ በቅርብ ተገኝቶ የቤት እንስሳ ይዞ በማጽናናት የህብረተሰቡ እገዛ የሚገለጽበት ነው። በዚህ የኩራ ሥርዓት ሌላው ክንውን በአካባቢው ሴቶች የሚከናወኑ የመደጋገፍ እንቅስቃሴዎች ናቸው። ይህም አንዲት ሴት ትዳር ስትመሰርት /ስታገባ/ በአካባቢዋ የሚገኙ ሴቶች ወተት ቅቤና የተለያዩ ምግቦችን በመያዝ ከጐኗ መሆናቸውን የሚገልጹበት መንገድ ሲሆን በተጨማሪም ቤትዋን የምትሠራበትን ሰሌን በማዋጣት የድርሻቸውን የሚያበረክቱበት እሴት ነው። ይህ ማህበራዊ ባህላዊ ሥርዓት እንደ ማህበራዊና ባህላዊ ግዴታ ስለሚታይ ከፍተኛ የመተጋገዝና የመረዳዳት ባህሪይ ያለው ነው። በዚህ ማህበራዊ መስተጋብር ያለመሳተፍና ከመረዳዳት ወደኋላ ያለ ሰው በማህበረሰቡ ዘንድ ይነቀፋል፣ ይወገዛል።

በአፋር ብሔረሰብ «ፈኢማ» የተባለ እሴትም አለ። በአፋር ዕድሜና ጾታን መሠረት አድርጎ የሚፈጠር አደረጃጀት ፈኢማ ይባላል። በየአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች የየራሳቸው ፈኢማ ያላቸው ሲሆን በዚህም የአዋቂዎች፣ የሴቶች ፣ የወጣቶች ፈኢማዎች በመባል እንደየአረጃጀታቸው በየአካባቢያቸው የሚከናወኑ ተግባራትን በማስተባበር የላቀ ሚና ይጫወታሉ። በየአደረጃጀቶቹ የሚገኝ እያንዳንዱ ፈኢማ በአባላቱ የተመረጠ መሪ /ፈኢማ አባ/ አለው። የወጣቶች ፈኢማ በማህበረሰቡ ውስጥ ሕግና ሥርዓት የማስከበር ሚና ሲኖረው አባላቱም በፈኢማ-አባ /መሪ/ ይመራሉ። በእያንዳንዱ አደረጃጀት የተመረጠ ፈኢማ አባ /መሪ/ አባላቱን የመምከር፤ ሲያጠፉ የመቅጣት ሥልጣን ያለው ሲሆን ማህበረሰቡን እርስ በርሱ እንዲደጋገፍ የማስተባበር ኃላፊነትን ይወጣል። በሴቶች ፈኢማ የምትመርጥ መሪ /ፈኢማ አባዋ/ በአባላት መካከል ትስስር እንዲኖር የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲጠናከር ትሰራለች። በተለይም በደስታና በሀዘን ጊዜ የማስተባበር ኃላፊነትዋን ትወጣለች። በአጋጣሚ ግጭት ቢፈጠር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የማድረግ ሚና አላት። የወጣቶች ፈኢማ አባላት ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲመጣ ወደ አዋቂ ፈኢማ ይሸጋገራሉ።

በአፋር ማህበራዊና ባህላዊ መስተጋብር ውስጥ «ኦላ» የሚባል እሴት አለ። ኦላ በግለሰቦች ግንኙነት ደረጃ ማህበራዊ ትስስር የሚፈጠርበት ሥርዓት ነው። ኦላ ሲባል ለይምሰል ሳይሆን ጥልቅ የሆነ ወዳጅነት የሚጠናከርበት ሂደት ነው። ይህም በአጋጣሚ ወይም ታስቦበት የሚፈጠር የወዳጅነት ትስስር ነው። ኦላ በአጋጣሚ ተገናኝተው ወይም አንዳቸው ከሌላው ጋር ወዳጅነት መመሥረት ፈልገው በተመራረጡ ሰዎች መካከል የሚፈጠር ወዳጅነትን የሚገልጽ ነው።

ሁለት ግለሰቦች ወዳጅነት ለመመስረት ከወሰኑ በኋላ ይህን ወዳጅነታቸውን በይፋ ለማሳወቅ ምስክር ወይም እማኝ የሚሆኑ ትልልቅ ሰዎች በተገኙበት ሁኔታ በባህላዊ ሥርዓት የሚገናኙበት አግባብ ይፈጠራል። ይህ ግንኙነት የሚመሠረትበት ሥርዓት ኦላ ይባላል። በዚህ ሁኔታ የሚፈጠር ወዳጅነት ዘላቂ በመሆኑ ከግለሰቦቹ ባለፈ በቤተሰቦቻቸው በኩልም ትስስር ይፈጠራል። ይህ ባህላዊ ሥርዓት በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሲሆን ከዝምድና ትስስር ባልተናነሰ ጠንካራ ግንኙነት የሚፈጠርበት እሴት ነው።

በአፋር ብሔረሰብ ውስጥ በሠርግ ወቅት የሚከናወንና በሠርግ ምክንያት የሚፈጠር የትስስር ባህላዊ ሥርዓት ደግሞ «አለጊና» ይባላል። አለጊና በአብዛኛው የሚዜዎች ኃላፊነት የሚገለጽበትና ወሳኝ ሚናቸውን የሚወጡበት ነው። በሠርግ ወቅት በሙሽሮቹና በሚዜዎቹ መካከል የተፈጠረውን ጠንካራ ትስስር እንዲቀጥል በማድረግ እና ጥንዶቹ ትዳር መስርተው በጋብቻ ተሳስረው ህይወት መምራት ቢጀምሩም የሚዜዎቹ ሚና አይቋረጥም፤ በጥንዶቹ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር በማድረግና በባልና ሚስቱ መካከል አለመግባባት ሲፈጠርና ግጭት ሲኖር ችግሩን በመፍታት ትዳር እንዳይናጋ በትኩረት ይሠራሉ። በዚህ ረገድ የሚዜዎቹ ሚና ቀላል አይደለም። አለጊና በሠርግ የተጀመረውን ግንኙነት በዘላቂነት እንዲቀጥል በማድረግ በሁሉም ዘንድ የሚታወቅ ሥርዓት ነው።

ከትዳር ምሥረታ በኋላ ልጅ ሲወለድ በስም አወጣጥ ላይ የሚከናወነው የአፋር ባህላዊ ሥርዓት ደግሞ «ሙጋኢና» ይባላል። በአፋር ብሔረሰብ ልጆች ሲወለዱ የሚካሄደው የስም አወጣጥ /ሂደት/ ቤተሰባዊ ብቻ ሳይሆን ከዘመድም ባለፈ ወዳጅ የተባሉ ግለሰብ በመጠሪያ /ስም/ የህፃኑ /የህፃኗ/ ስም ለማውጣት የሚሰባሰቡበት ወይም በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የሚሳተፉበት አሠራር ነው። የአንድ ልጅ ስም በእናት ወይም በአባት ሲወጣ መጠሪያው የአንድ ዘመድ ወይም ወዳጅን መጠሪያ ስም በመውሰድ ነው። የዚህ ልጅ መጠሪያ ስም ዋናው መነሻ የሆነው ግለሰብ ወይም የልጁ ስም በስሙ የተሰየመለት ግለሰብ በአካባቢው ባይኖር /ባይገኝ/ መረጃው ወዲያውኑ በዳጉ የመረጃ ልውውጥ ሂደት ይደርሰዋል። ወይም ይሰማል። በዚህ ባህላዊ ሥርዓት በስሙ ልጅ የተሰየመለት ግለሰብ ይህን ከሰማበት ጊዜ ጀምሮ ለቤተሰቡ ያለው ክብርና ፍቅር ይጨምራል። በሙጋኢና ሥርዓት የሚከናወነው የልጅ ስያሜ ከሁለት ቤተሰቦች ባለፈ በማህበረሰቡ መካከልም ወዳጅነትን ያጠናክራል።

በአፋር ብሔረሰብ አንድ ጐሳ ከሌላው ጐሳ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት የሚጠናከርበት ማህበራዊና ባህላዊ ሥርዓት ደግሞ «ኦፌሂና» ይባላል። ኦፌሂና ማለት ሰላማዊ ሁኔታ መፍጠር በሰላም ለመኖር ስምምነት ላይ መድረስ ማለት ነው። ግጭት ቢፈጠር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የሚደረግበት ሥርዓት ነው። በጐሳዎች መካከል አፌሂና ከተከናወነ በምንም ሁኔታ ግጭት እንዳይፈጠር ወይም እንዳይቀጥል ጥንቃቄ ይደረጋል።

«ዳጉ» የሚባለው እጅግ በጣም የታወቀና አስፈላጊ የሆነው ዋናው የመረጃ ልውውጥ ማህበራዊና ባህላዊ ሥርዓት ነው። አንድ ሰው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲጓጓዝ ለሚያገኘው ሰው መረጃ ሳይሰጥ አያልፍም። በመንገዱ ያጋጠመውን ወይም ያየውን ወይም የሰማውን የሰውም ሆነ የአካባቢ ሁኔታ ይናገራል። የዳጉ መረጃ ልውውጥ ፈጣን ነው። ቶሎ ይዛመታል፣ ይዳረሳል፣ በቅብብሎሽ ህዝቡ ነገሮችን ለማወቅ አይዘገይም። አሁን – አሁን ከአፋር አልፎ በሌሎች አካባቢዎችም እየተለመደ መጥቷል። ዳጉ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል የሚጠቀስ አሠራር ነው። በአጭሩ በጣም ጠቃሚና አስፈላጊ የመረጃ ማዳረስ ሥረዓት ነው።

/ምንጭ፡- የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያዘጋጀውን ጥናት ጠቅሶ ጋዜጠኛ ግዛቸው ሙሉጌታ በፌዴሬሽን ድምጽ መጽሄት የቀረበ።/

 

ግርማ ለማ

 

 

Published in አጀንዳ
Saturday, 02 December 2017 17:46

ህዝብና መንግስት ይደማመጥ!

 

ህዝብና መንግስት መተማመንና መደማመጥ አለባቸው።ህዝብና መንግስት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ መሆን ካልቻሉ ልማቱም ዕድገቱም የታሰበው ደረጃ አይደርስም።መደማመጥ ካልተቻለ የመልካም አስተዳደር ችግሩ፣ኪራይ ሰብሳቢ ከመቀነስ ይልቅ ጡንቸኛ እየሆነ ይሄዳል።ይሄ ደግሞ ህዝብን ለአመፅና ለቅራኔ ያነሳሳል።ነገር ግን መንግስት የሰራውን፣ እየሰራ ያለውን፣ወደፊት የሚሰራውን በግልፅ ለህዝቡ ባሳወቀ ቁጥር ልማቱ እንኳን ሁሉንም ህብረተሰብ በሚፈልገው ደረጃ ተጠቃሚ ባያደርግም ነገን ተስፋ በማድረግ ለቀጣዩ የልማት ስራ ይተጋል።ብልሹ አሰራሮች ሲኖሩም በጊዜው ነቅሶ እያወጣ እንዲታረሙ ይገፋፋል።መንግስትም የሚመራውን ህዝብ የሚያከብር ነውና የቀረቡለትን ቅሬታዎች በወቅቱ ይፈታል።በአጥፊዎችም ላይ የማስተማሪያ ቅጣት ይጥላል።በዚህ ጊዜ ህዝብና መንግስት መተማመናቸው እየጎለበተ ይሄዳል።በአንድ ጉዳይ ላይ አንድ አይነት ቋንቋ መነጋገር ይችላሉ።

ለዚህ ደግሞ ሁሉም መንቀሳቀስ አለበት።መደራጀት አለበት፤መሰረታዊ ጥቅሞቹን ለማስከበር መታገል አለበት።የአካባቢው አስተዳደርም ይሁን በየደረጃው ያለ አመራር ሲያጠፋ መገሰጽ መቻል አለበት፤ኪራይ ሰብሳቢነት፣ሙስና እና ብልሹ አሠራር ውስጥ ሲገባ፣ጉቦ ሲቀበል እያየ ዝም ማለት የለበትም።በአጠቃላይ አመራሩ የተስተካከለ እንዲሆን ህዝቡ ሞጋች መሆን አለበት።

ይህን ለማስተካከል በተናጠል መሮጥ አያዋጣም።ህዝቡ በተደራጀ መንገድ መንቀሳቀስ አለበት። ህዝብ ሲደራጅ የአካባቢው አስተዳደር የሚያደርጋቸው መጥፎ ዝንባሌዎችን ፊት ለፊት መታገል ሲጀምር ያ አመራር የህዝቡን መሰረታዊ ጥቅሞች እያስከበረ መሄድ ይጀምራል።የህዝቡ ትግል ሲቀዛቀዝና የተደራጀ ተሳትፎው ሲቀንስ በየደረጃው ያለ አመራር ሃይ ባይ አመራርና የሚታገለው ህዝብ ስለማይኖር ለሙስና እና ብልሹ አሠራር የተጋለጠ ይሆናል። ስለዚህ በዋነኛነት የሚያስፈልገው የተቀናጀ የህዝብ እንቅስቃሴ ነው።ይሄ ሲሆን ነው መልካም አስተዳደር የሚሰፍነው። የፌዴራል ስርዓቱ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ወደኋላ እንዳይቀለበስ ለማድረግ የሚቻለው።ስለዚህ ህዝቡ ጠንካራ ትግል ማድረግ አለበት።ይሄ የሚሆነው ደግሞ በለዘብተኝነት ሳይሆን በጠንካራ ትግል መሞረድ ሲቻል ነው።

መንግስትም ለህዝቡ ሲናገር መደመጥ አለበት።የሚሰራው የልማት ስራ የህዝብ ነው። የአገር ነው። የመንግስት ሚና የመሪነት ብቻ ነው።በተሰራው ተጠቃሚው ህዝብ ነው። የሚያድገው አገር ነው። ስለዚህ መንግስት በሚያቅዳቸው፣በሚያነሳቸው ሀሳቦች፣ በሚጠይቃቸው ሀላፊነቶች በሌሎችም ቦታዎች ህዝብ አቤት አለሁ ልማቱ የእኔ ነው ሊል ይገባል። አቤት ብሎም አፀፋውን መመለስ አለበት።

ህዝብ የተፈጥሮ ሀብቱን መንከባከብ ፣እያንዳንዱ አርሶ አደር ባለችው ማሳ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ተጠቅሞ፣የሙያተኛ ምክርን አክለው በየዓመቱ ከሚያመርቱት በእጥፍ ለማምረት መንቀሳቀስ መቻል ያስፈልጋል። አምራች ዜጋ ከሆኑና ሁሉን የሚያመርት ከሆነ የተትረፈረፈ ምርት ይመጣል። ይሄ በተገኘ ቁጥር የገቢ ምንጩ ይጨምራል።ከዛ ባሻገር ሸማቹ ህብረተሰብ በተመጣጠነ ዋጋ ምርት መግዛት ይጀምራል።ምርቱ አነስተኛ በሆነ ቁጥር ራሱ ሸማቹም አይጠቀምም።ስለሆነም ምርቱን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን ከምርቱ ጋር የተሳሰሩ ግብዓቶችን መጠቀም መቻል አለበት።ቴክኖሎጂዎችን ማላመድና መጠቀም ያስፈልጋል።የእንስሳት ሀብቱን በዘመናዊ መንገድ ማልማት ይገባል።በዚህ መንገድ ሀብት ሲጨምር፥ህዝብ የጥቅሙ ተጋሪ እየሆነ ሲሄድ የበለጠ ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓቱ እየጎለበተ የሚሄድበትን ሁኔታ ይፈጥራል።

አሁን በአንዳንድ ቦታዎች የሚታየው ግጭት በየአካባቢ ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የማልማት ሥራ ባለመሰራቱ፤ እንዲሁም ህብረተሰቡ አንድነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ተከታታይ የሆኑ የአስተምህሮ ሥራዎች ባለመሰራቱ የተፈጠሩ ናቸው።ይሄ በሂደት እየተስተካከለ የሚሄዱ ይሆናሉ። ይሄንን እርግጠኛ ለመሆን የተጠናከረ ስራ መስራት ከመንግስት ይጠበቃል።የፌዴራል ስርዓቱን ጥቅሞች ማስረዳት ህብረተሰቡ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው የማድረግ ስራ መስራት ያስፈልጋል።ይሄ ሲሆን መንግስትና ህዝብ ይግባባሉ ፤ይረዳዳሉ። ለኢትዮጵያ ህዳሴም አሁን ካለው በላይ ይተጋሉ።

ይህን ውጤታማ ለማድረግ በመንግስት ደረጃ የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መጠናከር አለበት።ማንኛውም በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ የሚመጣን ችግር ለመመከት ዋናው ጉዳይ የህዝብና የመንግስት መደማመጥ መኖር ነው።ስለዚህ መንግስት ከህዝቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ያዳምጥ። አዳምጦም ፈጣን ምላሽ ይስጥ።ይሄ ከሆነ ህዝብ የሚጎረብጠው ነገር እንኳን ቢያጋጥመው ከመናገርና ከመታገል ወደ ኋላ አይልም። ህዝብና መንግስት መደማመጥ ከቻሉ ተአምር ይፈጥራሉ።ስለዚህ የህዝብና የመንግስት መደማመጥ ያስፈልጋል።

 

 

 

 

 

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ

 

አዲስ አበባን ጽዱ፣ ውብና አረንጓዴ ለማድረግ በተያዘው ዕቅድ መሰረት ነዋሪውን የሚያሳትፍ ቋሚ የጽዳት ፕሮግራም ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የአስተዳደሩ ሥራ አስኪያጅ ቢሮ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቆንጂት ደበላ ትናንት እንዳስታወቁት፣ አዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እያደገች ከመምጣቷ ጋር ተያይዞ በግለሰብ እና በተቋማት ደረጃ የሚመነጩ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች ከተማዋን እየበከሉ ናቸው፡፡

በመሆኑም የከተማዋ ነዋሪ በጽዳቱ ተሳታፊ የሚያደርግ የህዝብ ንቅናቄ ከህዳር 22 እስከ 26 በተለያዩ ወረዳዎችና ክፍለ ከተማዎች የሚካሄድ ይሆናል፡፡ በዚህም 70 ሺ የሚጠጉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ነዋሪዎች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ የጽዳት ፕሮግራሙ ህዳር 30 ቀን 2010.ም በይፋ የሚጀመር ሲሆን በየወሩ መጨረሻ ቅዳሜ በቋሚነት የሚከናወን መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ፣የበርካታ አገራት ኤምባሲዎች እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚኖሩበት ከተማ ከመሆኗ አንፃር የሚጠበቅባትን ያህል ውብ፣ ጽዱና አረንጓዴ አይደለችም ያሉት ኃላፊዋ ከተማዋ የሚመጥናትን ዕድገትና ውበት እንዲኖራት ህዝቡን ያሳተፈ የጽዳት ንቅናቄ ይደረጋል ፡፡

ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች ከአካባቢው ነዋሪ እና ከተለያዩ ተቋማት እንደሚ መነጩ የተናገሩት ወይዘሮ ቆንጂት ህዝብን ያሳተፈ ንቅናቄ መደረጉ ለጽዳቱ ዘመቻ ቆሻሻ አመንጪውን አካል ባለቤት ለማድረግ በመታሰቡ ነው፡፡ በዚህም የከተማው ነዋሪ በአካባቢው እስከ ሃያ ሜትር ርቀት የሚያጸዳ ሲሆን የግልና የመንግሥት ተቋማት እስከ ሃምሳ ሜትር ርቀት የማጽዳት ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል፡፡

 

ሰብስቤ ኃይሉ

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።