Items filtered by date: Sunday, 03 December 2017
Sunday, 03 December 2017 21:18

ሴካፋ ዛሬ ይጀመራል

 

በኬንያ አስተናጋጅነት ከዛሬ ጀምሮ በዘጠኝ የክልሉ ሀገራት መካከል በሚደረገው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ (ሴካፋ) የሚካፈለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 27 ተጫዋቾችን በመያዝ ላለፉት ሰባት ቀናት ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል። የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለም ከስብስቡ ላይ አራት ተጫዋቾችን በመቀነስ ወደ ውድድሩ የሚያቀናውን የመጨረሻ ቡድናቸውን ይፋ አድርገዋል።

በግብ ጠባቂ በኩል ታሪክ ጌትነት (ደደቢት)፣ በረከት አማረ (ወልዋሎ)፣ ተክለማርያም ሻንቆ (ሀዋሳ ከተማ) ተመርጠው ወደ ስፍራው ያቀኑ ሲሆን በተከላካይ መስመር ሰባት ተጫዋቾች ወደ ስፍራው ሄደዋል። እነዚህም ቴዎድሮስ በቀለ (መከላከያ)፣ አበበ ጥላሁን (ሲዳማ ቡና)፣ አበባው ቡጣቆ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ግርማ በቀለ (ኤሌክትሪክ)፣ አምሳሉ ጥላሁን (ፋሲል)፣ ተመስገን ካስትሮ (አርባምንጭ ከተማ)፣ ሄኖክ አዱኛ (ጅማ አባ ጅፋር) ናቸው። አማካዮች ሳምሶን ጥላሁን (ኢትዮጵያ ቡና)፣ ተስፋዬ አለባቸው (ወልዲያ)፣ ከነአን ማርክነህ (አዳማ)፣ እንዳለ ከበደ (አርባምንጭ)፣ ብሩክ ቃልቦሬ (ወልዲያ)፣ ፍሬው ሰለሞን (ሀዋሳ ከተማ) ተመርጠዋል። በአጥቂ ስፍራም አቡበከር ሳኒ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ አብዱራህማን ሙባረክ (ፋሲል ከተማ)፣ አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)፣ ዳዋ ሁቴሳ (አዳማ ከተማ)፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል (መቐለ ከተማ)፣ አቤል ያለው (ደደቢት)፣ ፀጋዬ ብርሀኑ (ወላይታ ድቻ) በስብስቡ ተካተዋል።

ዋልያዎቹ ከሶስት ቀን ቀደም ብለው ወደ ናይሮቢ አስር ሰዓት በፈጀ ጉዞ ማቅናታቸው ታውቋል። በምዕራብ ኬንያ ከዋና ከተማዋ 360 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው ካካሜጋ ተጉዘዋል። ዋልያዎቹ ወደዚህ ውድድር ሲጓዙ ተገቢው ትጥቅ ሳይሟላላቸው እንደሆነ የተለያዩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ ነበር። ይሁን እንጂ ፌዴሬሽኑ ተገቢውን ትጥቅ አሟልቶ እንደሚልክ ገልጿል።

ውድድሩ ዛሬ ተጋባዧ ሊብያ ከታንዛኒያ ጋር በምታደርገው ጨዋታ ሲጀመር ሰኞ በ8 ሰዓት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከብሩንዲ አቻው ጋር በካካሜጋው ቡክሁንጉ ስታዲየም የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታውን የሚያከናውን ይሆናል። ዋልያዎቹ በዚህ ውድድር በምድብ ሁለት ከቡሩንዲ፤ ኡጋንዳና ዚምባቡዌ ጋር መደልደላቸው ይታወቃል።

2017ቱ የምስራቅ እና መካከለኛው ዋንጫ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከተጋበዙ 2 ቡድኖች አንዱ የሆነው እና ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ ለ ተደልድሎ የነበረው የዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድን ራሱን ከውድድሩ እንዳገለለ አስታውቋል። የዚምባቡዌ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይፋ እንዳደረገው ከሆነ በኬንያ ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የተነሳ ለተጫዋቾቹ ደህንነት አስተማማኝ ዋስትና ማጣቱን በውድድሩ ላለመሳተፉ በምክንያትነት አስቀምጧል። ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ ጨዋታዎች ከብሩንዲ፣ ዩጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ጋር ብቻ የሚገናኝ ይሆናል።

 

ቦጋለ አበበ

Published in ስፖርት

አትሌት የማነ ጸጋዬ በፎኮካ ማራቶን ለአሸናፊነት ይጠበቃል፤

 

በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ አገራት የጎዳና ላይ ውድድሮች እንደሚካሄዱ ይታወቃል። በዛሬው ዕለትም ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር እውቅና ያገኙና የወርቅ ደረጃ የተሰጣቸው የማራቶን ውድድሮች የሚካሄዱ ይሆናል። ጃፓን በየዓመቱ የምታዘጋጀው የፎኮካ ማራቶን ዛሬ ለ71ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት አግኝተዋል።

በውድድሩ ተሳታፊ ከሆኑት አትሌቶች መካከል ፈጣን ሰዓት ያለው ኢትዮጵያዊው አትሌት የማነ ፀጋዬ የአሸናፊነቱን ግምት በከፍተኛ ደረጃ በማግኘት ቀዳሚው ሆኗል። የ32ዓመቱ ፀጋዬ የግሉን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበው እ..አ በ2012ቱ የሮተርዳም ማራቶን ሲሆን፤ አሸናፊ ለመሆንም 2:04:48 የሆነ ሰዓት ነበር የፈጀበት። አትሌቱ ያለፈው ዓመት በዚሁ የፎኮካ ማራቶን ተሳትፎ በማሸነፍ፤ በማራቶን ውድድሮች ተሳታፊነትም ዘጠነኛውን ስኬት ማስመዝገብ የቻለበት ሆኗል። በወቅቱ ርቀቱን ለመሸፈን የፈጀበትም 2:08:48 የሆነ ሰዓት ነበር።

ያለፈው ክረምት በተካሄደው የለንደን የአትሌቲክስ ዓለም ሻምፒዮና ላይ አገሩን ቢወክልም እንዳልተሳካለት የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ውድድር ላይ ያለውን ልምድና ተሞክሮ ተጠቅሞ የአሸናፊነቱን ክብር በድጋሚ ያገኛል የሚለው ግምት አይሏል። ፀጋዬ በዛሬው ውድድር ላይ ለአሸናፊነት የሚሮጥ መሆኑን በሰጠው አስተያየት፤ «ጥሩ ልምምድ በማድረጌ አሸናፊ እንደምሆን ልበ ሙሉ ነኝ» በማለት ገልጿል።

በዚህ ውድድር ላይ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራቱ ኬንያ፣ ኤርትራ እና ኡጋንዳ አትሌቶች ለኢትዮጵያዊው አትሌት ፈተና እንደሚሆኑም ይጠበቃል። ከኢትዮጵያዊው አትሌት የዘገየ ሰዓት በማስመዝገብ ሁለተኛው ፈጣን አትሌት የተባለው ኡጋንዳዊው አትሌት ስቴፈን ኪፕሮች ነው። እ..አ የ2012ቱ ኦሊምፒክ እንዲሁም የ2013ቱ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባለ ድል የሆነው ኪፕሮች በጃፓን ያስመዘገበው2:06:33 የሆነ ሰዓት ፈጣን በሚል ተመዝግቦለታል። ኬንያውያኑ አትሌቶች ላኒ ሩቶ፣ ቢዳን ካሮኪ እንዲሁም ኤርትራዊው አትሌት አማኑኤል መሰል ባላቸው ፈጣን ሰዓት ለአሸናፊነት አሊያም ለብርቱ ተፎካካሪነት የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው።

በፎኮካ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ሲሆን፤ አትሌት ገዛኸኝ አበራ ከአሜሪካዊው ፍራንክ ሾርተር ቀጥሎ በውድድሩ ለሦስት ጊዜያት ተሳትፎ በማሸነፍ ታሪካዊ አትሌት ነው። የቦታው ክብረወሰን የተመዘገበው ኢትዮጵያዊው አትሌት ፀጋዬ ከበደ እ..አ በ2009 የገባበት 2:05:18 የሆነ ሰዓት ነው። ፀጋዬ የቦታው የሁለት ጊዜ አሸናፊ በመሆንም ከገዛኸኝ ቀጥሎ ሊቀመጥ የሚችል ነው። የማነ ፀጋዬም የዛሬውን ውድድር የሚያሸንፍ ከሆነ ክብረወሰኑን ከፀጋዬ ከበደ ጋር የሚጋራ ይሆናል።

በተመሳሳይ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው የሲንጋፖር ማራቶን የሚካሄድ ይሆናል። በዚህ ውድድር ላይም ኬንያውያኑ አትሌቶች በሁለቱም ጾታ የአሸናፊነት ግምቱን በከፍተኛ ደረጃ ያገኙ ሆነዋል። ሳይፕሪያን ኮቱት በውድድሩ ላይ ከሚሳተፉት አትሌቶች ፈጣን ሰዓት ያለው አትሌት ሲሆን፤ 2:07:11 ያለፈው ዓመት የፓሪስ ማራቶንን ሲያሸንፍ ያስመዘገበው ሰዓት ነው።

አትሌት ደረጀ ደበሌ እና አበበ ነገዎ ደግሞ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ይሆናል። የ31ዓመቱ ደረጀ እ..አ በ2013 ያስመዘገበው 2:07:48 የሆነ የግሉ ምርጥ ሰዓት ያለው አትሌት ነው። አትሌቱ ያለው ሰዓት ከኬንያዊው አትሌት በሰከንዶች የዘገየ በመሆኑም የአሸናፊነት ግምቱን አጠናክሮለታል። ደረጀ ያለፈው ዓመት የካቲት ወር ያስመዘገበው ሰዓትም 2:10:23 ነው። እ..አ የ2015 የሮም ማራቶን አሸናፊው አትሌት አበበ በበኩሉ 2:08:46 በርቀቱ ያስመዘገበው ምርጥ ሰዓቱ ነው።

 

ብርሃን ፈይሳ

 

 

Published in ስፖርት

2018 የክረምት ኦሎምፒክና ፓራ ኦሎምፒክ ጨዋታ ሊጀመር ከመቶ የሚያንሱ ቀናት ብቻ ይቀሩታል፡፡ ይህን ተከትሎ ጨዋታውን ለማስተናገድ የተመረጠችው የደቡብ ኮሪያዋ ፒዮንግቻንግ ከተማ ሥራ በዝቶባት ከርሟል፡፡ የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አካልም ከተማዋ እያደረገች ያለውን ዝግጅት ለመገምገም ከነሐሴ 29 እስከ ነሐሴ 31 ቀን በፒዮንግቻንግ የመጨረሻ ጉብኝቱን አድርጓል፡፡

ከዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በተጨማሪም የደቡብ ኮሪያ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ የክረምት ስፖርት ፌዴሬሽኖች ተወካዮችና ስፖንሰሮች እንዲሁም የተለያዩ አገራት ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች በግምገማው ተካፍለዋል፡፡ የግምገማ ጉብኝቱም የተለያዩ ቦታዎችን ያካተተ ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል ለአትሌቶች በመኖሪያነት የሚያገለግሉ የኦሎምፒክ መንደሮች የሚገኙበት በጋንግኒዩንግ ከተማ ጠረፍ ላይ የሚገኘው የጋንግኒዩንግ ኦሎምፒክ ፓርክ እና በፒዮንግቻንግ- ጋንግኒዩንግ ፈጣን የባቡር መስመር ላይ ዋነኛ መተላለፊያ ሆኖ የሚያገለግለው አዲሱ የጅንቡ የባቡር ጣቢያ ይገኙበታል፡፡

የከተማዋ ዝግጅት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና በጉብኝታቸው መርካታቸውንም የጉብኝቱ ተሳታፊ አካላት መስክረዋል፡፡ የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አስተባባሪ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ጉኒላ ሊንድበርግ፣ ፒዮንግቻንግ የ2018 የክረምት ኦሎምፒክን ለማስተናገድ እያደረገች ያለችውን ዝግጅት አድንቀ ዋል፡፡ «የክረምቱን ኦሎም ፒክና ፓራ ኦሎምፒክ ጨዋታ ዎች በስኬት ለማስተናገድ አዘጋጅ ኮሚቴው በሚገባ መዘጋጀቱን ባደረግነው ጉብኝት ለመገንዘብ ችለናል» ብለዋል፡፡ አዘጋጅ አካላቱ በበኩላቸው «ከሞላ ጎደል ዝግጅታችን አጠናቀናል» እያሉ ነው፡፡

አጠቃላይ የዝግጅቱ ሂደት

ከደቡብ ኮሪያ ኤምባሲ የተገኘ መረጃ እንደሚያመላክተው፤ አዘጋጆቹ ለውድድሩ መሰረታዊ የሆኑ ሁሉንም መሰረተ ልማቶችና ግብዓቶች ከሞላ ጎደል አዘጋጅተው አጠናቀዋል፡፡ በውስጡ የፒዮንግቻንግ ኦሎምፒክ ስታዲየምን፣ ትልልቅ ኮርፖሬት ስፖንሰሮች ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያሳዩበት አዳራሽ፣ የአትሌቶች የመልበሻ ክፍልንና ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን ያቀፈ የፒዮንግቻንግ ሁለገብ ህንጻ ግንባታ ዘጠና በመቶ ተጠናቋል፡፡ ሰላሳ አምስት ሺህ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለውና የኦሎምፒኩን የመክፈቻና መዝጊያ ሥነ ሥርዓቶች የሚያስተናግደው ታሪካዊው የፒዮንግቻንግ ስታዲየም ግንባታ የተጠናቀቀውም ያለፈው የጥቅምት ወር መጀመሪያ አካባቢ ነው፡፡

ደቡብ ኮሪያውያን መለያችን ነው የሚሉት የአልፔንሲያ ስካይ የዝላይ ማዕከልም እንደዚሁ ግንባታው ተጠናቆ የጨዋታውን መጀመር እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ አሥራ ሦስት ሺህ ተመልካቾችን ማስተናገድ የሚችለውና እንደ አሸን የሚበዙትን የፒዮንግቻንግ ተራራዎች እንደ ልብ ማየት የሚያስችሉ ረጃጅም ማማዎች የተሰሩለት ለዓይን ማራኪው የአትሌቲክስ ማዕከል ህንጻም ጨዋታዎችን ለመመልከት ወደ ፒዮንግቻንግ ለሚሄዱ የተለያዩ አገራት ጎብኚዎች ዋነኛ መዳረሻ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ ህንጻ ወደ መንሸራተቻ ስፖርት፣ የጠመንጃ ተኩስና የአገር አቋራጭ ሩጫ ስፖርት ማዕከላት የሚወስዱ መግቢያ በሮች የሚገኙበት ነው፡፡ የጋንግኒዩንግ የበረዶ መንሸራተቻና የፈረስ ግልቢያ መዝናኛ ማዕከልም ከጥቂት ጥቃቅን የማጠናቀቂያ ሥራዎች በስተቀር ግንባታው በመገባደድ ላይ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም ጨዋታዎች ተጀምረው እስኪጠ ናቀቁ ድረስ እየበራ የሚቆይ የኦሎምፒክ ችቦ የሚቀመጥበት ግዙፍ ታሪካዊ መቅረዝ እየተገነባ ይገኛል፡፡ ፒዮንግቻንግ እየገነባቸው ያለው ይህ የኦሎምፒክ ችቦ ማብሪያ መቅረዝ ዲዛይን እስከ ውድድሩ መክፈቻ ጊዜ ድረስ በጥብቅ እየተጠበቀ በምስጢር ተይዞ የሚቆይ ይሆናል፡፡

በኦሎምፒክ ዝግጅት የቱሪዝም መዳረሻነት

የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት የክረምት ኦሎምፒኩ ፒዮንግቻንግ በዓለም አቀፉ የቱሪዝም ካርታ ውስጥ ቦታ እንዲኖራት ያደርግልናል የሚል ተስፋ አላቸው፡፡ ለዚህም ከዚህ ቀደም ይህን መንገድ ተጠቅመው በዓለም የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ ዕውቅና ማግኘት የቻሉትን የጃፓኗን ናጋኖ እና የኖርዌይዋን ሊልሃመር ከተሞች በማስታወስ ተስፋቸውን ያጠናክራሉ፡፡ ይህንን ህልማቸውን ለማሳካትም ኮሪያውያኑ ለቱሪስት ፍሰቱ መሳለጥ መሰረታዊ በሆኑ የመሰረተ ልማትና የግብዓት አቅርቦት ሥራዎች ላይ አተኩረው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ለአብነትም ኦሎምፒኩ በሚካሄድበት ወቅት ለጎብኚዎች ፈጣን የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል ፒዮንግቻንግን ከዋና ከተማዋ ሴዑል የሚያገናኝ ፈጣን የባቡር መስመር እየተገነባ ነው፡፡

የባቡር መስመር ግንባታው ኦሎምፒኩ ከመጀመሩ በፊት በተያዘው ህዳር ወር ላይ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይህም የፒዮንግቻንግን የክረምት ኦሎምፒክ ለማየት ወደ ደቡብ ኮሪያ የሚሄዱ ጎብኚዎች ኢንችዮን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከደረሱ በኋላ ከሁለት ሰዓታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ፒዮንግቻንግ መድረስ እንዲችሉ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ መልኩ ፒዮንግቻንግን አዲሲቷ የኮሪያ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ከምንጊዜውም በላይ ለቱሪዝም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ የ2018ቱን የፒዮንግቻንግ የክረምት ኦሎምፒክና ፓራ ኦሎምፒክ ልዩ ገፅታ ካላበሱት ነገሮች መካከል አንዱ ያደርገዋል፡፡

አንድ ጎብኚ ከሚፈልጋቸው መሰረታዊ አቅርቦቶች መካከል የሆቴል አገልግሎት ቀዳሚው ነው፡፡ የፒዮንግቻንግ የክረምት ኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴም ከአስተናጋጇ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን የምግብና የመጠጥ ማዘዣ ዝርዝሮች በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉመው እንዲዘጋጁና በአገሪቱ በሚገኙ 2200 ሆቴሎችና ምግብ ቤቶች እንዲሰራጩ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህም ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ማንኛውም የውጭ አገር ጎብኚ የሚፈልገውን የምግብና መጠጥ መስተንግዶ በራሱ ቋንቋ ማዘዝ እንዲችል የሚያደርግ ሲሆን፤ የ2018ቱን የፒዮንግቻንግ የክረምት ኦሎምፒክ ልዩ ያደርገዋል፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡም ትህትናና ጨዋነት የተላበሰ እንዲሆን ለሠራተኞች ልዩ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡

በፒዮንግቻንግ አዲስ የግንባታ ቴክኖሎጂ

የፒዮንግቻንግን የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ልዩ የሚያደርገው ነገር አዘጋጆቹ ኦሎምፒኩ ከተካሄደ በኋላ በቀላሉ ሊነሱና ለሌላ አገልግሎት ሊውሉ የሚችሉ የመሰረተ ልማት አተካከልና የግብዓት አቀራረብ አሰራር ዘዴዎችን መከተላቸው ነው፡፡ በዚህም ለኦሎምፒኩ ሲባል በጊዜያዊነት የተገነቡ ህንጻዎችና ጥቅም ላይ የዋሉ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ጨዋታዎች እንደተጠናቀቁ በቀላሉ የተወሰነ ማሻሻያ ተደርጎባቸው ከስፖርት ውጭ መደበኛ አገልግሎት ወደ መስጠት ሥራቸው ይገባሉ፡፡ ሌላው ይቅርና ከኦሎምፒክ አደባባይነት ውጭ ሌላ አገልግሎት መስጠት የማይችለው የኦሎምፒክ አደባባይ እንኳን ያለምንም ጉዳት በፍጥነት ለማፍረስና ቦታውን እንደገና ጥቅም ላይ ለማዋል በሚያስችል ዲዛይን ነው የተሰራው፡፡

በአጠቃላይ ፒዮንግቻንግ እያደረገችው ያለውን የ2018 የክረምት ኦሎምፒክ ልዩ ዝግጅት የአዘጋጅ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት ሚስተር ሊ ሂቢዮም፣ «እስካሁን ከተደረጉት ሁሉ የተሻለ የክረምት የኦሎምፒክ ጨዋታ በማዘጋጀት ደቡብ ኮሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስፖርትን ለመምራትና አዲሲቷ የእስያ የክረምት ስፖርቶች ማዕከል ለመሆን ያላትን ብቃት ለዓለም ማሳየት እንፈልጋለን፤» በማለት ገልጸውታል፡፡

 

ይበል ካሳ

 

 

Published in ስፖርት

 

ኢትዮጵያውያን በስም አወጣጥ ላይ ለየት የሚያደርጋቸው የራሳቸው ባህሪ አላቸው። ያው የዛሬ የዛሬውን ልጅ ስም ሳይጨምር ማለቴ ነው። ምክንያቱም የዛሬው ትውልድ አባት እናቱ ያወጣለትን ስም እንዲጠራበት አይፈልግም። በዚያም ቢጠራ በዘመንኛው ቋንቋ «ፋራ ነህ» ይሉኛል በሚል እሳቤ ይፈራላ። ስለዚህም ፋራ ከሚባል ይልቅ አለመቀበልን ወይም በዚያ ስም ያለመጠራትን ይመርጣል። በዚህም ይመስላል ብዙዎች በፍርድ ቤት ስማቸውን ለማስቀየር ሲሯሯጡ የምንመለከተው። በአንድ ጊዜ ሦስት አራት ስምም የሚያስወጣ ይኖራል።

ግን እንደሚመስለኝ ለዚህ ጉዳይ ዋነኛ መንስኤው በማንነት ያለማመን ጉዳይ ነው። በእርግጥ ስምና ምግባር አብረው ተያይዘው የሚጓዙ ናቸው ለማለት እቸገራሉሁ። ምክንያቱም ማንኛውም ሰው በስሙ ልክ ሲጓዝ አልታየም። ተግባራትን ሲያከናውንም በወጣለት ስም መነሾ አይደለም። በቃ ስንቱን ላንሳላችሁ ማንም በስሙ ተግባሩ ይገለጻል ብዬ አላምንም። ነገር ግን ስም ሲወጣ አባት እናት ልጃቸው ይሆናል ብለው የሚያስቡትን ሊመርጡ ይችላሉ፤ ከሁነቶች ጋር አቆራኝተውም እንዲሁ ሊያወጡት ይችላሉ።

በአጋጣሚም አንድ ክስተት ተፈጥሮ ከዚያ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ኖሮትም ስማችን የወጣልን ብዙ ሰዎች ልንኖር እንችላለን። ነገር ግን ብዙዎቹ አሁን ዘመነኛ ከሆነው ነገር ጋር እንዲዛመድ ብቻ ይፈልጋሉ። በእርግጥ ለልጅ ስም ማውጣቱ ቀላል ስለማይሆን በዘመኑ ታዋቂ ወደሆነው ጉዳይ ማድላቱ የግድ የሚሆንበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል። ትክክለኛውን መርጦ ለመሰየምም የሚቸገሩበት ሁኔታ ይፈጠራል። ስለዚህ ወላጆች ከፊልሞች፣ ከድራማዎች፣ ከልቦለዶች፣ ከቴሌቪዥን እና ሬዲዮኖች ያገኙትን ስም ቀልባቸው ስለተሳበ ብቻ ከወደዱት ስም ጋር ያላትሙናል። ከዚያማ ትርጉሙን የማናውቀው፣ ያልለመድነውንና ለምን እንደወጣልን የማንረዳውን ስም ይዘን እንጓዛለን።

ምዕራባውያኑ በዚህ በኩል ለሕዝባቸው ጥሩ ነገር አስቀምጠዋል። የሕፃናት ስሞችን ዝርዝር እና ትርጉም የሚያትቱ መጻሕፍት እና ድረ ገፆች አሏቸው። ስለዚህም ወላጅ የሚፈልገውን ስም ትርጉም በየዓይነቱ መርጦ በመመልከት ለልጁ ስም ያወጣል። እኛ ጋር ግን ይህ ስለሌለ ስሞችን ባለማወቅና ባለመረዳት ደስ ስለሚል ብቻ ተወስደው ጥቅም ላይ ይውላሉ። እንደው ይህ ብቻ ስለሆነ ነው ብሎ ቢጠየቅ መልሱ አዎ እንደማይሆን ዕሙን ነው። ምክንያቱም እንደ ቀድሞዎቹ አባትና እናቶች መጸሐፍ ቅዱሳዊ ትርጓሜ ያለውን ስም መሰረት ተደርጎ ስሞችን ማውጣት ስለሚቻል።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያዊ ሕፃናት ስሞችን ስንመለከት በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ይዘት እንደሌላቸው እንረዳለን፤ አብዛኞች ስሞች ቅላፄያቸው ለጆሮ እንዲጥሙ እንጂ፤ ታሪኩ ምን ማለት ነው ብለን ብንጠይቅ መልስ የሚሰጥ አይኖርም፤ ልጆቹም ቢሆኑ እንጃ የሚል መልስ ነው የሚሰጡት። ይህ ደግሞ የባህል ወረራ ተጽዕኖ መሆኑ በግልጽ የሚያሳይ ነው። ወላጆችም ቢሆኑ በዚህ ዙሪያ ብዙ ትኩረት እየቸሩ እንዳልሆነ አመላካች ነገር አለ። ለምሳሌ ልጃቸው አበበች ተብላ ከምትጠራ አንድ የውጪ አገር ዜግነት ያላት ሴት ስም መጥቶ ስያሜው ቢሰጣትና በዚያ ብትባልላቸው ያስደስታቸዋል። ለልጆቻቸውም ዛሬ ላይ የሚያወጡት ስም ከዚሁ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ትስስር ያለው ነው። ያው አንዳንዶች ባህል ጠባቂዎችን ሳይጨምር ማለቴ ነው።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ወላጆች የልጃቸው ስም አጠር ብሎ፣ ሲጠሩት አፍ ላይ ደስ የሚል፣ ዜማ ያለው፣ ሲያሞካሸሽም የሚጥምና እርካታን የሚሰጥ እንዲሆን ለማድረግ ይጥራሉ፤ ትርጓሜም እንዲኖረው ይሻሉ። ለምሳሌ የጥንት የኢትዮጵያውያንን ስም አወጣጥ ስንመለከት ሃይማኖት ትልቅ ድርሻ ነበረውና ይበልጥ ትርጉሙ ገኖ እንዲወጣ ይደረግ ነበር። ከታሪክ ጋር ተዋዶ፣ አገርኛ ፀጋ አላብሶ፣ የራሷን አሻራ ትቶ ስም እንዲወጣ ይደረጋልም። አገራዊ ባህል ከሥሩ ሳይነቀል ዘመን ተሻግሮ እንዲቀጥልም ተደርጎ ነው በልብ ላይ የሚታተመው።

ይህ ትውልድም ይህንን የቆየ ኢትዮጵያዊ አሠራር ቢጠቀምበት ባህሉን፣ ማንነቱን እንደጠበቀ ለልጆቹም የሚያስተላልፍ ይሆን ነበር። «ስሜ የወጣው ከዚህ ነው፤ ትርጓሜውም እንዲህ ነው» እያለ ቢጓዝ የራሱን ባህል፣ ያውም ከዕምነቱ ጋር በምንም መልኩ የማይጋጨውን፣ በጦር ሜዳ ያላጣውን ነፃነት በሰላሙ ዘመንም እንዲሻገርና ኃያልነቱን እንዲያገኝ ያደርገው ነበርም። ይሁንና ይህንን ልምድ ያላደረገ ማህበረሰብ እየዳበረ በመሆኑ ስሞቻችን ቅጥ እያሳጣቸው ነው። እንደውም በዚህ አጋጣሚ አንድ የገጠመኝን ነገር ላውጋችሁ። ነገሩ እንዲህ ነው።

አንድ ቀን ሦስት ህፃናት ተሰበሰበው ሲጓዙ አገኘኋቸውና የእያንዳንዳቸውን ስም እንዲነግሩኝ ጠየኳቸው። እነርሱም እንኳን ልጠራው ሰምቼው የማላውቀውን ስም ይደረድሩልኝ ጀመር። የኢትዮጵያን ስም ያለው አባታቸው ላይ ሲደረስ ነው። የአንዱ ልጅማ እስከ አያቱ ሄጄ እንኳን ኢትዮጵያዊ ስም አላገኘሁም። ወዲያው ብስጭት አይሉት ንዴት ምን አይነት ስሜት እንደተሰማኝ ባልተገነዘብኩት ሁኔታ ለመሆኑ ኢትዮጵያዊ ነህ ስል ጠየኩት። ከትከት ብሎ ሳቀብኝና «ታዲያስ» አለኝ። በጣም ገረሞኝ ጉዞዬን ቀጠልኩ እላችኋለሁ። ታዲያ ይህ ሁኔታ እስከመቼ መቀጠል አለበት ትላላችሁ? መልሱን ለእናንተው ልተወውና ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስ። ሥራ ቦታ ላይ ስማችን ወሳኝነት አለው። ግልጽ፣ ከደንበኛም ሆነ ከሌሎች ሠራተኞች ጋር አብሮ ለመሥራት ነገሩን ቀለል የሚያደርግ አጠር ያለ ስም ቢኖረን መልካም ነው። በአጭሩም ሲጠሩ ብዙ የሚከብዱ መሆን የለባቸውም። ባህላዊ ማንነትን የሚያንጸባርቁ ቢሆኑ ደግሞ ይበልጥ ይመከራል። በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ገጠመኝ ላውጋችሁ። መልካም ሥራ የምትባል የሥራ ባልደረባዬ ነች። የምትፈልገውን መረጃ ለመቀበል ወደ አንድ ቦታ ስልክ ትደውላለች። ከዚያኛው በኩል ስልኩን ያነሳው ሰው የምትፈልገውን መረጃ ካቀበላት በኋላ ስሟን ይጠይቃታል። እርሷም «መልካም ሥራ» ስትል ትመልስለታለች። አሜን ካለ በኋላ አሁን መልሶ ስሟን ይጠይቃታል። ደግማ ትመልሳለች። በመጨረሻ መናገር አልፈለገችም ወይም ደግሞ በትክክል አውቆት ይሁን ተሰናብቷት ስልኩን ዘጋው እላችኋለሁ።

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ስሞቻችን ሰላምታን እንኳን የሚሰብኩ መሆን እንዳለባቸው ነው። በእርግጥ የማህበረሰባችን አረዳድ ብዙም የሰፋ ስላልሆነ የሚያደናግሩ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ። ነገር ግን ስሞች ሰባኪና አስተማሪ መሆን እንደሚገባቸው መገንዘብ ግድ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ቅጽል ስም ለማውጣት እንድንገደድ ይሆናል። ይህ ደግሞ ፈጽሞ የመዝገብ ስሙን እንድንሰርዝ ያደርገናል። ስለሆነም ባህል እና ታሪክ ያለን ሕዝቦች ስለሆንን ታሪካችንን ሳንለቅ ስማችንን ልንሰይም ይገባናል። ነገር ግን ባህላችንን እና ታሪካችንን ያለውን ጥቅም በቅጡ መረዳት ካልቻልን ልክ ታሪክ እንደሌላቸው ሕዝቦች የራሳችንን እየጣልን የሩቁን ለማግኘት መሞከራችን አይቀሬ ነው። ቀጣይ ትውልዱም ታሪኬ ወዴት ነው ሲለን የምንመልሰው እናጣለን። ስለዚህ ይህ አካሂድ መቀየር አለበት ሳልል አላልፍም።

አንድ ሕፃን ሲወለድ ታሪካዊና ቤተሰባዊ ሁኔታን ለማስታወስ ስም እንደሚሰጠው ይታወቃል። ስለሆነም የድሮዎቹ ስሞች ከዚህ በኋላ በሕያው ሕፃን ስምነት ጥቅም ላይ ሲውሉ መመልከት ይቻላል ይሆን? ምክንያቱም “የትልቅ ሰው ስም፣ የትልቅ ሰው ስም” እየተባሉ ይቀለድባቸዋልና ነው። አንድ የሂሳብ ትምህርት መምህሬ ነበር። ስሙ ማን እንደሆነ ታውቃላችሁ? «ቅደም ተከተል ለጥቅ» ይባላል። የጉዞን ቅድመ ሁኔታ በማመላከት የወጣለት ስም ነው። በዚህ ደግሞ ስማቸው የሚያስገርም የሆኑ ሰዎችን እንድናስብ ያደርገናል። ለአብነት አብዛኛው ጎጃም አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ሁነቶችን መነሻ በማድረግ የሚሰጡ ስሞችን መጥቀስ በቂ ይመስለኛል ። እንደ አንቺነሽ ገነቱ፣ ይሁን በቃሉና... የመሳሰሉትን። በእርግጥ እስካሁን ያነሳኋቸው ሁሉ የሰዎች መጠሪያ ስሞችን በሚመለከት ነው። ነገር ግን ስም ሲነሳ በርካታ ነገሮች መኖራቸው ግልጽ ነው። ከዚህ ካለፍን ደግሞ በርካታ መጠሪያ ስሞችን መጠቆም ያስፈልጋልና ትኩረቴ ከዚህ እንዳይወጣ ገድቤዋለሁ። በዚህ መነሻነት ለሌሎች ተግባራት የምናወጣቸውንም ስሞች መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ ከግንዛቤ እንዲገባም እሻለሁ። ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንደሚባለው አሁን ይዘነው በምንጓዘው የስም አወጣጥ ዘዴ ከቀጠልን ማንነታችንን እናጣለን፣ ታሪክና ባህልም አይኖረንም። ስለዚህ በስማችን እኛነታችንን እናሳይ፣ በስማችን ተግባራችንም ይገለጽ። በአጠቃላይ በስማችን እኛን እንሁን እያልኩ ሀሳቤን ልቋጭ። ሠላም!

 

ፅጌረዳ ጫንያለው

 

 

Published in መዝናኛ

የቅርስና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ መግቢያ ከመቼውም ይልቅ አሸብርቋል። ባህላዊ የሆነው የቡና ሥርዓቱን የጠበቀ የቡና አፈላል ዘዴ ገና ከመግቢያው ጀምሮ ይታያል። ቄጤማው ተጎዝጉዞ፣ እርቦ ላይ ደግሞ ተወዳጁ ፈንድሻ ቃሙኝ ቃሙኝ ይላል። በተለይ ደግሞ በመሶብ ውስጥ ተደርጎና ብርሌን በሚተካው ፕላስቲክ ውስጥ ተቀምጦ የሚታየው ጠጅ ባህልን በአካል ቦታ ተሰብስቦ የማየት ኃይልን ይፈጥራል። መቼም ይህ የሆነው በማን ነው ማለትዎ እንደማይቀር አምናለሁ።

የዛሬ የህይወት እንዲህ ናት እንግዳዬ ናቸው ይህንን ተግባር የከወኑት። እንግዳዬ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የተዘጋጀውን መርሃግብር አብነት በማድረግ እስከ አስተናጋጆቻቸው ድረስ እንደ አውዱ እንዲያሸበርቁ አድርገው ነው ዝግጅታቸውን የሚያቀርቡት። በጣም ባህል ወዳድ መሆናቸውንም የተመለከትኩት በዚሁ ድርጊታቸው ነው። አቀራረባቸው፣ አለባበሳቸው፣ የማስተናገድ ችሎታቸው ሁሉ ሳይወዱ በግድ እንዲወዷቸው ያደርጎዎታል። እኔም የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚዬምን ለመገንባት በቀረበው ጥናት ላይ ለመሳተፍ ስጓዝ በአፄ ምኒልክ ወቅት ምን አይነት አለባበስ እንደነበር በዓይነ ህሊናዬ እንድስል አድርገውኛል።

እኒህ እንስት ወንዱም ሆነ ሴቷ በባህላዊ አልባሳት አሸብርቀው እንዲያስተናግዱ ያደርጓቸዋል። ይህ ሲሆን ደግሞ በወቅቱ በነበረው ባህላዊ አገልጋዮች ዘንድ የሚለበሰውን አልባሳት እንዲለብሱ በማድረግ ነው። እናም ይህ ተሞክሮአቸውና ሌሎች የሚያደርጓቸው ተግባሮቻቸው ስለሳቡኝ የህይወት እንዲህ ናት አምዳችን እንግዳ እንዲሆኑ ጠየኳቸው። እርሳቸውም ያለምንም ማቅማማት ፈቃደኝነታቸውን ስለሰጡኝ እንካችሁ ልምዳቸውን ተጋሩ አልኳችሁ።

ልጅነት

እንግዳዬ ወይዘሮ አጸደ ተክሌ ገብሩ ሲሆኑ፤ ታህሳስ 29 ቀን በ1964 .ም በትግራይ ክልል ማይጨው ከተማ ነው የተወለዱት። በልጅነታቸው ከቤተሰቡ ውስጥ ፈጣንና አደርገዋለሁ ብለው ያሰቡን ለማድረግ የሚሞክሩ ናቸው። እናትና አባታቸው በውትድርና ዘርፍ ውስጥ የሚሰሩ ስለነበሩና በካምፕ ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ስለሆኑ ልጃቸውን ብዙም የሚያዩበት አጋጣሚ አልነበረም። ስለዚህም እንግዳችን ጫና ስላልነበረባቸው ብዙ ነገር የመሞከርና የማድረግ እድሎችን እንዲያገኙ ሆነዋል። እንደውም በአንድ ወቅት ገና የ14 ዓመት ልጅ እያሉ ከተማ ሄደው ለቤት መሸፈኛ የሚሆን ቆርቆሮ ገዝተው እንደመጡ ያስታውሳሉ። በዚህ ደግሞ ቤተሰቦቻቸው ልዩ ስም እንዳወጡላቸውና «ቀውጢ» ብለው ይጠሯቸው እንደነበር አጫውተውኛል።

እንግዳችን ወይዘሮ አጸደ ያው የወታደር ልጅ ከመሆናቸው የተነሳ ይሁን ወይም ደግሞ የተሰጣቸው ተሰጦ ይኑር በግልጽ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም በጠዋት መነሳትን ልምዳቸው ያደረጉት ገና በልጅነታቸው ጀምሮ ነበር። ፍራቻም ቢሆን በእርሳቸው ዘንድ ቦታ አይሰጠውም። ሁሉንም ነገር በድፍረት የሚያደርጉና ውጤታማ እንደሚሆኑበት የሚያምኑ ናቸው። ይህ በመሆኑም ብዙ ጊዜ በጠዋት በመነሳት ወንዝ ወርደው ውሃ ይቀዳሉ። በአቅማቸው ትንሽ ገንቦ ቢሰጣቸውም ትልቁን ካልያዝኩ ብለው ያስቸግራሉ። ያም ተሰጥቷቸው የታዘዙትን ውሃ በቦታው ያደርሳሉ።

ቅዳሜና እሁድ ሲመጣ ደግሞ የአካባቢው ልጆች ተሰብስበው የቤተሰቦቻቸውን ልብስ በመያዝ ወንዝ ወርደው ያጥባሉ። በዚህ መካከል ደግሞ ያው ልብሱ እስኪደርቅ ድረስ ጨዋታ ይኖራልና በርካታ ወጎች፣ የጨዋታ አይነቶችና መሰል ተግባራትን ያከናውናሉ። በተለይም ቤተሰብን ለማስደሰት እበት ለቅመው ቤት ድረስ ይዘው በመምጣት ቤቱን ያሳምራሉ። ማይጨው በወቅቱ ምንም እንኳን ከተማ ብትሆንም ባህላዊ ማንነቷ ግን ያልጠፋባት ስለሆነች ብዙዎቹ የአካባቢው ሴቶች እንደ ገጠሩ ማህበረሰብ ልጅ ሁሉ ሙያቸው የላቀ ነው። ለዚህም ይመስላል እንግዳችንም ከልጅነታቸው ጀምሮ ስፌት የመስፋት ሙያ የነበራቸው። ዛሬም ላይ የሚጠቀሙባቸው ሰፌዶች፣ መሶብወርቆችና ሌሎች ቁሶች በእራሳቸው የእጅ ጥበብ የተሰሩ ናቸው።

የትምህርት ሁኔታ

እንግዳችን ወይዘሮ አጸደ ትምህርታቸውን «» ብለው የጀመሩት በዚያው በትውልድ ቀያቸው ማይጨው ውስጥ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም ማይጨው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። ከዚያም ከወንድማቸው ዘንድ ለመኖር ወደ ደሴ ተጉዘው ነበርና ወይዘሮ ስሂን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። 12ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቁም ከዚያ ለቀቁና አዲስ አበባ ገቡ። የራሳቸውን ሥራ በመስራትም ደፋ ቀና ማለቱን ተያያዙት። ለጊዜው ብዙ ገንዘብ አልነበራቸውም። ከባለቤታቸው ጋርም ተጣልተው ስለነበር ከ150 ብር ውጪ በእጃቸው የለም። ስለዚህ አንድ ሥራ ለመጀመር ቢያንስ 500 ብር መያዝ እንዳለባቸው ያምናሉ።

እናም በጣም የሚወዷትን ያገለገለች ቁም ሳጥናቸውን በማደስ ይሸጣሉ። ያንን ብርም በመያዝ ቤት ይከራያሉ። ለቤቱ የሚከፍሉት ብር ከሥራ ማስጀመሪያቸው ጋር ተጣጥሞ ስለማይሄድላቸው ሥራቸውን ዝቅ ካለ ደረጃ መጀመር እንዳለባቸው አምነው ጉልትን መረጡ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ነበር ከብዙ የውጪ ዜጎች ጋር ለመግባባት የሚያስችል አቅም እንዲኖራቸው ኮሌጅ መማር እንዳለባቸው ያሰቡት። እናም አደረጉት። ኮሌጅ በመግባትም የርቀት ትምህርት በመከታተል ዲፕሎማቸውን በእንግሊዝኛ ትምህርት አጠናቀቁ። ከዚያ ግን ትምህርታቸውን መቀጠል አልቻሉም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ኃላፊነት ስለተጫነባቸው ነው። በእርግጥ እርሳቸውም ቢሆኑ ከውጪ ዜጎች ጋር ያለምንም መደናገር ንግግር እንዲያደርጉና የንግድ ስራቸውን እንዲያስፋፉ ስለፈለጉ እንጂ መማርን ስለፈለጉት አልነበረም ይህንን ያደረጉት። የሆነው ሆኖ ግን ተምረውታል።

የጉልት ህይወት

እንግዳችን ከላይ እንደተባለው ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው ባዷቸውን ስለነበሩ ሥራ ለመጀመር የሚያስችላቸው ገንዘብ የላቸውም። እናም ይህቺን ጉልት በተከራዩበት ቤት በር ላይ በመደርደር ነበር እንዲጀምሩ የተገደዱት። ይህን ሲያደርጉ ደግሞ በጣሙን የሚያስገርም ተግባራትን እየተቆናጠጡ ነው። ይኸውም ከፒያሳ አትክልት ተራ ድረስ በማዳበሪያ የገዙትን አትክልት በጀርባቸው በማዘልና በእጃቸው ጭምርም በመያዝ እስከ ሳር ቤት ድረስ በመጓዝ ነው። ምክንያቱም ለታክሲ የሚከፍሉትን ለንግዱ ያደርጉታል፤ ባስ እንዳይዙ ደግሞ ያንን ያህል አትክልት አይጭንላቸውም። ስለሆነም ይህንን ተግባር የዘወትር ሥራቸው አድርገውት ቆይተዋል።

ከዚያ ጎን ለጎንም ሌሎች ተግባራትን ያከናውናሉ። ይኸውም የድለላ ሥራን ነው። «ስራን ለሰሪው እሾህን ላጣሪው» እንዲሉ ሁሉም በየመስኩ በሚሰማራበት ሙያ ውጤታማ ለመሆን መልፋቱ የተለመደ ነውና እርሳቸውም ስራቸውን ማከናወን ያለባቸው በቢሮ ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን መተዳደሪያ በመፍጠር ነው። ይህ ደግሞ ጠቀሜታው ከእርሳቸው አልፎ ለሌሎች ጭምር እንደሚሆን ያውቃሉ። የድለላ ሥራ ከሰዎች ጋር መግባባትን ይጠይቃል። ለራስ መታመንና ትዕግስትንም ይሻል። ይህም ብቻ አይደለም ሙያው ጥንቃቄና ብልሀት ካልታከለበት አንዳንዴ ለእንጀራ ብለው የሰሩት ሥራ ክስን አስከትሎ ተጠያቂ ሊያደርግ ይችላል። ቤተሰብንም እስከ ማሳጣት መድረሱ አይቀሬ ነው።

እንግዳችን ግን በዚህ የሚፈተኑ አይደሉም። ምክንያቱም አስተዳደጋቸው ነጻነቱን ሰጥቷቸው። ያመኑበትን ተናግረውና ፈጣን ሆነው ብዙ ነገር ሰርተውበታልና። ስለዚህ ባለታሪካችን የሙያውን ክፉና በጎ መስመር ሁሌም የሚያልፍበት ስልት ዘይደው ይንቀሳቀሳሉ። ብዙውን ጊዜ በድለላ ሙያ የሚሰማሩት ወንዶች ቢሆኑም ለወይዘሮ አጸደ ግን የተለየ ተግባር አይደለም። እንደውም በራስ የመተማመን ስሜትን ይበልጥ ጨምሮላቸዋል። በርካታ ደንበኞችንም አፍርተውበታል። ጥቂት የማይባሉት አንዳንድ ወንድ ደላሎች እንኳን ሁል ጊዜ ከእርሳቸው ጋር መስራትን እንዲሹ ያደረጉበትን አቅም እንዳጎለበቱ አውግተውኛል።

እንግዳችን ወይዘሮ አጸደ የቤተሰብ አስተዳዳሪና የሁለት ልጆች እናት ቢሆኑም አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ለልጆቻቸው እርካታን ይሰጣሉና ገንዘብ ይገኝባቸዋል ብለው በሚያስቧቸው ሥራዎች ላይ ነው። የሚያከናውኑት ተግባር የዕለት እንጀራቸው ነው፤ ገቢው ቤታቸውን ደጉመው ልጆቻቸውን ያሳድጉበታል። ለትምህርትና ለቤት ኪራይ ወጪም ቢሆን የእርሳቸውን እጅ ጠባቂው ብዙ ስለሆነ በሥራ ላይ መታተርና የተለያዩ ተግባራትን መከወን ግዴታቸው ነው።

ለልጆቻቸው የተለየ አክብሮትና ፍቅር አላቸውና ምንም እንዲጎልባቸው አይሹም። ስለዚህም በችግር ውስጥ እያለፉም ቢሆን ልጆቻቸውን ያስደስታሉ። በእርግጥ እንግዳችን ይህንን የድለላ ሥራ ሲያከናውኑ ደላሎቹ ባመጧቸው ሰዎች አማካኝነት ነው። እርሳቸውን የሚፈልጓቸው የማስተርጎም ሥራ እንዲያከናውኑላቸው ነው። ስለዚህ የሚሸጠው ወይም ደግሞ የሚከራየውን ቤት በማሳየትም ሆነ ደላሎቹን በማገዝ ይሳተፋሉ። እውቀታቸው ሌላ ተግባርም እንዲከውን አድርገውታል። በየቤቱ እየተዘዋወሩ ልጆችን ለማስጠናት ይጠቀሙበታል።

እንዲያስጠኑላቸው የሚጠይቁም አንዳንድ ሰዎች አሉና እርሳቸውም ምንም ሳያቅማሙ ይቀበላሉ፤ ምክንያቱም ገንዘብ ማግኛ ዘዴ ነዋ። ቀን የዘወትር ተግባራቸው የሆነውን የጉልት ንግድ እንዲሁም የድለላ ሥራ ሲያጧጡፉ ይቆዩና ማታ ላይ ደግሞ እረፍት ያስፈልገኛል ሳይሉ ወደ የሚያስጠኗቸው ልጆች ዘንድ ያመራሉ። ይህን ሥራቸውን የተመለከቱና በሥራ ታታሪነታቸው የተሳቡት አንዳንድ የአካባቢያቸው ነዋሪዎችም ለምን በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ አትደራጂም የሚል ምክርን ይለግሷቸዋል።

እርሳቸውም ይህ ሀሳብ እፎይታን ይሰጠኝ ይሆናል በሚል እምነት ተደራጅተው መስራትን ይጀምራሉ። አሁን መንግሥት ለጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ በሰጠው ሸድ ውስጥ የማቀነባበር ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ። የማር አምራች ማህበራት አባልም እንዲሆኑ አገዛቸው። ንቦችም አሏቸው። 28 አይነት አረቄም ያመርታሉ። ብዙዎችንም ለኤምባሲዎችና አከፋፋዮች ያስረክባሉ። በሥራቸውም 17 ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ እድል ፈጥረዋል። ከዚህ በፊት ግን ወር እንኳን ሳይሰሩ የተሰጣቸውን ሸድ ከነ እቃው ጎርፍ ይወስደዋል። ባዷቸውንም ያስቀራቸዋል። ለቀለብና ለቤት ኪራይ እጃቸው ይበልጥ ያጥራቸዋል። ነገር ግን ከዛሬ ነገ ይሻላል በሚል ተስፋ ትንሽ ለመቆየት ይሞክራሉ። ጎናቸው የነበሩ ሰዎችም የተለያዩ እገዛዎች ያደርጉላቸዋል። ይሁንና ሁለት ህጻናት ልጆቻቸውን ማረፊያ ጥግ አጥተው ተንከራተቱ። እርሳቸውም ችግር ውስጥ ወደቁ።

ዛሬ ነገ ክፍለ ከተማው አንድ መፍትሄ ይሰጠኛል ብለው ቢጠብቁም መፍትሄ ታጣ። በችግር የኖረው ቤተሰብ ተስፋ ይባስ ተሟጠጠ። ስለዚህ ሌላ አማራጭ መፈለግ እንዳለባቸው አመኑ። ሲገኝ ተቃምሰው ሲጠፋ ጦም አድረው ለመኖር ወደ ቢሾፍቱ ተጓዙ። በዚያም በአነስተኛ ወጪ ቤት ተከራይተውም ጠጅ እየጣሉ ለከተማው ነዋሪ እያቀረቡ አንድ ዓመት አሳለፉ። የሆነው ሁሉ ሆነና አዲስ ተስፋ አዲስ ለውጥ በቤት ውስጥ ሰፈነ። ድህነት ቦታውን ለቆ መካከለኛ ገቢ ላይ ካሉት ተርታ አሰለፋቸው። ሥራው ለብቻ የሚከናወን ስላልሆነም ለሌሎች እድል በመፍጠር የተለያዩ ሰራተኞችን አሳተፉ።

«አሁን ተስፈኛ ነኝ፤ አቃቂ ቃሊቲ አካባቢ ሸድ ተሰጥቶኝ እየሰራሁ ነው። በቀጣይም መንግስት ደግሞ በቀጣይ ኢንዱስትሪ የምመሰርትበትን 1500 ካሬ ሜትር ቦታ ሰጥቶኝ ሥራውን ለመጀመር እየተንቀሳቀስሁ ነው። ሦስት አይነት ሥራ ለመስራት ፈቃድ አውጥቻለሁ። ስለዚህም በእነዚህ ዘርፎች ሁሉ ጠንካራ ሰራተኛ እሆናለሁ። ሌሎችም ከእኔ እኩል ሰርተው እኔ የደረስኩበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ እተጋለሁ። ከእኔ ችግርም እንዲማሩና ለውጥ እንዴት እንደሚመጣ እንዲረዱ እንዲሁም እንዲማሩ አደርጋሉ» የሚሉት እንግዳችን፤ በችግር ውስጥ ማለፍ ሁልጊዜ እንደሚያስተምራቸውና አዳዲስ ተግባራት እንዲያከውኑ እንደሚያደርጋቸው ይናገራሉ።

እንደውም ቢሾፍቱ ከመሄዳቸው በፊት ቂርቆስ ላይ የተሰጣቸው ሸድ በጎርፍ እንደተወሰደ ትተውት መሄዳቸው ጥሩ ደረጃ ደርሰው ራሳቸውንም ለውጠው እንዲመጡ እንዳገዛቸው አስረድተው፤ ይሁንና በዚህ ቦታ ቆይተው ቢሆን ኖሮ በእርሳቸው ስም የተመዘገበው ሸድ መቼም ተስፋ ሳይሰጣቸው ችግር ውስጥ ከቷቸው እንደሚቆይ ነግረውኛል። ለዚህም በምክንያትነት ያነሱት ከዓመት ቆይታ በኋላ ሸዱ በአንቺ ስም ስለሆነ የሰራሽበትን ክፈይ ተብለው ከ2000 ብር በላይ መክፈላቸውን ነው።

ባህል ወዳድነት

ማሸብረቅና ደምቆ መታይት በማንም ዘንድ የሚወደድ ተግባር ነው። ነገር ግን ዘመን አመጣሽ አለባበስን መርጦ ብቻ መልበስ ተገቢ አይደለም። እንደ አቅምና እንደ ባህላችን እንዲሁም እንደ እድሜያችን ባህላዊ ልብስ መልበስን ያስፈልጋል። ዘመን አመጣሽ አለባበስ ቅጥ ሲኖረው ነው ተወዳጅነቱ የሚጨምረው። ለአብነት አሁን ላይ የሚሰሩ ባህላዊ አልባሳት ከውጪ ከሚመጡ ብጣቂዎች እጅግ ይልቃሉ። ስለዚህም በአገራችን ባህል እናሸብርቅ የሚለውን መልዕክት ሁል ጊዜ እንዲተላለፍና ሁሌም በውስጣቸው የሰረጸ እንደሆነ የሚገልጹት እንግዳችን፤ «እኔ መቼም ቢሆን በአገሬ ምርት እኮራለሁ። ምክንያቱም በአገሬ ግብዓት ተጠቅሜ የፈጠራ ባለቤትነት መብትን/ፓተንት ራይትን/ ማግኘት ችያለሁ። የአዲስ ግኝት ወይም ፈጠራ ተሸላሚ እንድሆንም ረድቶኛል።» ይላሉም።

እንግዳችን ወይዘሮ አጸደ የሞሪንጋ፣ የነጭ ሽንኩርት አረቄን ጨምሮ 28 የሚደርሱ ባህላዊ የአልኮል መጠጦችን ቀለማቸው ሳይቀየር ተፈጥሯዊ ሆነው እንዲቆዩ አድርገው ያዘጋጃሉ። ይህ ደግሞ የሚሆነው ምንም አይነት ኬሚካል ሳይገባበት በማር ብቻ የቆይታ ጊዜውን በማራዘም ነው። ይህን ማድረግ የቻልኩት ደግሞ ለባህሌ ልዩ ትኩረት ሰጥቼ በመስራቴ ነው ያሉት። በአገሪቱ በርካታ ያልታወቁና ያልተለመዱ ባህሎች አሉ። ይሁንና የሚያወጣቸውና የሚያስተ ዋውቃቸው ግን የለም። ስለዚህ ባህልን አውቆ ለሌሎች ማስረዳት ጥቅሙ ከራስ ይጀምራልና ይህንን ማድረግ እንደሚገባ ነው ያጫወቱኝ።

ባህላችንን እኛ እያከበርነው አይደለም፤ ያለውን ጠቀሜታም ቢሆን ባለን ልክ እየተገነዘብነው አልመጣንም የሚሉት ወይዘሮ አጸደ፤ ብዙን ጊዜ ምርታቸውን የሚጠቀሙትና የሚወዱት የውጪ አገር ዜግነት ያላቸው መሆናቸውን ያስረዳሉ። ምንም አይነት ከቮድካና ውስኪ የሚለይ አልኮል እንደሌለውና እንደማይጎዳ እንዲሁም ኬሚካል ያልነካው መሆኑን የሚገነዘቡትም እነርሱ ናቸው። ለዚህም ደግሞ ዋና ምክንያቱ ያላቸው የሳይንስ እውቀት መሆኑ ቢታወቅም ተፈጥሯዊ ነገር እንደማይጎዳ ግን ማንም የሚረዳው ነው። ነገር ግን በአገር ሰው የሚሰራ በመሆኑና የተለየ ጥበብ የገባበት ነው ብለው ስለማያምኑ ምርጫቸው ሌላ ይሆናል ይላሉም።

ጥቅምት ለእርሳቸው ልዩ ወቅት ነው። ያው እንደሚታወቀው በአገርኛችን በጥቅምት አንድ አጥንት ይባል የለ። ይህ ደግሞ ብቻውን ሲሆን መልካም አይደለምና ሞቅ የሚያደርጉ ነገሮችን እንጠቀማለን። ከእነዚህ መካከልም ባህላዊ መጠጣችን የሆነው ጠጅ አንዱ ነው። እናም እንግዳችንም ይህንን ጠጅ ለማዘጋጀት የሚያስችላቸውን ማር የሚያፍሱበት ወቅት ይህ ስለሆነ መቀሌ ድረስ በመጓዝ ማራቸውን ይሰበስባሉ። ከጠጃቸው ሲተርፋቸው ደግሞ እንጀራ ማር ስለሚያመጡ በኪሎ 150 እና ከዚያ በላይ ይሸጣሉ። ገዢዎቻቸው ኢትዮጵያዊያን ብቻ አይደሉም። እስከ የመን ድረስ ያሉ ሰዎች የሚሳተፉበት ስለሆነም በብዛት ለንግድ የሚሆናቸውን ማር በዚህ ወቅት ይሰበስባሉ። በእርግጥ ባለታሪኳ አጸደ ንግዳቸው የሚያበቃው በማር ብቻ አይደለም፤ ቅመማ ቅመምም ያዘጋጃሉ፤ ለኤምባሲዎች ያስረክባሉ፤ ይሸጣሉም።

ባህልና ቱሪዝም በሚያዘጋጃቸው የተለያዩ ትርኢቶች ላይ የብሔረሰብ ባህልን በማስተዋወቅም ይሳተፋሉ። የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ በአገሪቱም ሲኖር ብዙ ጊዜ እንዲያሳተፉ ጥሪ ይቀርብላቸዋል። እናም እርሳቸውም የተባሉትን ተግባር በውጤታማነት ያጠናቅቃሉ። ወይዘሮ አጸደ ምንም እንኳን ብሔራቸው ትግራይ ቢሆንም የእያንዳንዱን ባህል ማንነት በማስተዋወቅና በማክበር እንዲሁም በመልመድ የሚያክላቸው የለም። በእያንዳንዱ ዝግጅት ላይ ባህልና ቱሪዝም ይጥራቸው እንጂ ሌሎች አካላት እንዲያውቁትና ስለ ዝግጅቱ ምንነት እንዲረዱ ከማድረግ አኳያ አውዱን ጠብቀው በማዘጋጀትም ይታወቃሉ።

የውጭዎች የእኛን ባህል ለማምጣት ሲሉ ተፈጥሮን ሳይሆን ሽቶና መሰል ነገሮችን ይጠቀማሉ። ይህም ቢሆን ሽታው ከተፈጥሮው ጋር መቼም አይገናኝም። ስለዚህም ብዙን ጊዜ የተፈጥሮ ውጤቶችን ተጠቅሞ ባህልን ማስተዋወቅ እጅግ ያስደስተኛል የሚሉት እንግዳችን፤ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ በሚካሄድበት ወቅት ቡና በማፍላቱ ተግባር ብዙ ጊዜ እንደተሳተፉና በሁኔታቸው ብዙዎች እንዳደነቋቸው እንዲሁም ኢትዮጵያዊነት ይህ መሆኑን እንዲገነዘቡ እንዳደረጉበትም ይናገራሉ።

በማር የቆይታ ጊዜን መጠበቅ የቻሉ

ማርን እንደ ነብሳቸው ይወዱታል፤ አድገው በታልም። በዚህም ደግሞ ያለውን አቅምና የሚሰጠውን ጥቅም በሚገባ መረዳት ችለዋል። ምክንያቱም በተለያየ መልኩ እያዘጋጁት የቆይታ ጊዜን የሚያራዝምበትን ዘዴ ዘይደውበታል። ከውጪ አገር ዜጎች የተለያዩ ልምዶችን እንደሚቀስሙ የሚገልጹት እንግዳችን፤ በተፈጥሮ የሚገኙ ነገሮች ላይ ብዙ መመራመርና አዲስ ነገር መፍጠር እንደሚያስደስታቸው ይናገራሉ። ስለዚህም ማርን በመጠቀም አረቄያቸውንም ሆነ የሚጠምቁትን ጠጅ የቆይታ ጊዜው እንዲራዘምና እንዳይበላሽ አድርገው ያዘጋጃሉ። የአልኮል ይዘቱም በምዘና ታውቆ ለሽያጭ እንዲቀርብ ያደርጋሉ። በዚህ ደግሞ አዕምሯዊ ንብረት የፈጠራ ባለቤትነት መብት ሰጥቷቸዋል። ከግል የፈጠራ ባለሙያዎች መካከል በመሆን በ2009 .ም ሽልማት እንዲበረከትላቸው አድርጓቸዋል።

መዝናኛ

ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በኋላ መተኛትን የማይወዱት ወይዘሮ አጸደ፤ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ሁልጊዜ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ። ከዚያ ሲመለሱም ገላቸውን በቀዝቃዛ ውሃ ይታጠቡና ማታ ሲጽፉት ያደሩትን የሥራ መዘርዝር በማንበብ ምን ምን ተግባራትን እንደሚያከናውኑ እቅድ ያወጣሉ። ማን ከምን መቅደም አለበት የሚለውንም ይለያሉ። ይህንን በሚያደርጉበት ወቅት ግን ልጆቻቸውም ሆነ ጎረቤት ሲተኙ በጣም ይናደዳሉ። ምክንያቱም 12 ሰዓት ሙሉ እየተተኛ እንዴት መለወጥ ይቻላል? ብለው ስለሚያምኑ ነው።

ሰው በተለይ ከሌሊቱ ከ11 ሰዓት በኋላ መተኛት የለበትም፤ በማንኛውም መንገድ ሥራ ይጠፋል ተብሎ ስለማይታሰብ ለአብነት ግቢ እንኳን ማጽዳት ሥራ ነው። ታዲያ ለምን ይተኛልም ይላሉ። ለዚህም ይመስለኛል ተከራይተው በነበሩባቸው ቦታዎች ሁሉ አከራዮቻቸው እንዲወዷቸው የሆኑት። ሁል ጊዜም ግቢውን በማጽዳትና ምንም አይነት ቆሻሻ በአካባቢው እንዳይኖር በማድረግ ይታወቃሉ። እረፍት ሲፈልጉም ክራር በመጫወትና ልጆቻቸውን በማዝናናት ያሳልፋሉ። እንቅልፍን ላለመልመድ ሌሊት እንኳን ሳይቀር ክራር መጫወትንም እንደሚያዘወትሩ ይናገራሉ።

የክራር መጫወት ፍቅር የተጠናወታቸው ናቸው። ብስክሌት መንዳትም ቢሆን የሚያህላቸው አልነበረም። ሞተር ሳይክልም ቢሆን ይሞክራሉ። ይሁንና በአጋጣሚ ጉዳይ ተገልብጠው ጥርሳቸው ስለረገፈ ዛሬ ላይ ትተውታል። የእጅ ኳስ/ሀንድ ቦል/ ተጨዋችም ናቸው። ስለዚህ የተለያዩ ጨዋታዎችን ይችላሉ፤ ይጫወታሉም። ዛሬ ግን ከክራር ውጪ ሌሎቹን ለመሞከርና ለመጫወት ፋታ የላቸውምና ብዙ አይሰሩበትም።

ቤተሰባዊ ሁኔታ

«ሴት ሁለት ናት፤ ሴት የተለያዩ ሙያዎችን የሚቀዳጁ ሰዎች እናት ናት። ሴት በማስተዳደሩም ሆነ በመስራቱ ከተሳተፈች የሚያቅታት ነገር የለም። የጠንካራዎቹም እናት ሴት ናት» የሚሉት ወይዘሮ አጸደ፤ ምንም እንኳን ከባለቤታቸው ጋር ቢለያዩም ቤተሰባዊ ትስስራቸው ግን አሁንም እንዳለ ነው። ልጆቻቸውንም ቢሆን አስተምረው እራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ አስችለዋቸዋል። አንድ ግቢም ተከራይተው አብረዋቸው እየኖሩ ነው።

ሽልማቶችን

«የፈጠራ ሰው በሚል ተሸልሚያለሁ፤ ይህ የሆነውም የቆይታ ጊዜን በማር መጠበቅ ስለቻልኩ ነው። ጠላ ሲሰራ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ላይ ያለ ጥንስስ አይሆንም። በአንድ ቀንም አይደርስም። ነገር ግን እኔ በአንድ ቀን በጥቂት እህል ብዙ ማምረት ችያለሁ። ለምሳሌ ከ10 ኪሎ ገብስና ከሰባት ኪሎ ማር ከትንሽ ቅጠል ጌሾ 250 ሊትር አወጣለሁ። በጣዕምም ቢሆን ከአገረኛው ምንም ልዩነት የለውም። እንደውም ይህ የተሻለ ሆኖ ነው የተገኘው። በዚህ ደግሞ የፈጠራ ባለቤት በመባል ተሸልሜበታለሁ።» ሲሉም አጫውተውኛል።

ይህ ሥራቸው ደግሞ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አርባ ሺህ ብር፣ ዋንጫ፣ የእውቅናና የምስክር ወረቀት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እጅ እንዲረከቡ አድርጓቸዋል። ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁ በ2008 .ም ባካሄደው አውደ ርዕይ ላይ ሁለተኛ በመውጣታቸው ዋንጫን ተሸልመዋል። በዚሁ ዘርፍ በ2009 .ም አንደኛ በመውጣታቸው ዋንጫ አግኝተዋል።

ከደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮም ቢሆን እንዲሁ በሚያደርጉት ባህልን የማስተዋወቅ ሥራ የምስክር ወረቀት ተረክበዋል። በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮም እንዲሁ አድርጓል። እንግዳችን በሄዱበት አጋጣሚና በተገኙበት ስፍራ ሁሉ ከተለያዩ አካላት ሽልማትን አግኝተዋል። ይሁንና እርሳቸው ሁል ጊዜም እንዲህ ይላሉ። «ለሽልማት ብዬ አልሰራም። አገሬን ለማስተዋወቅ ግን ሁሌም እታትራለሁ። ዛሬም ነገም እስከ ህይወት ህልፈቴ ድረስ ይህንን አደርጋለሁ»። እንግዳችን ብዙ ያጋሩኝ ቁም ነገሮች ነበሯቸው። ነገር ግን ያው እንደሚታወቀው ጊዜና ቦታ ይገድባልና አባይን በጭልፋ እንዲሉ ጥቂቱን አንስቻለሁና ለዛሬ ያለኝን በዚህ ልቋጭ። መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ ብዬ ተሰናበትኩ።

 

ጽጌረዳ ጫንያለው

 

 

Published in ማህበራዊ

 

የሥነ-ራዕይ ጥበብ የሰብአዊነት ቀልብ፤ ህልም እና ቅዠት፤ ምኞት እና ተስፋ፤ ብሎም የዘመናት ህልፈት እና የትዝታ ምልሰት ማመላከቻ፤ የምናብ እና የዕውነታ ማሳያ ሰው ሰራሽ የተንቀሳቃሽ ምስሎች ሁለንተናዊ ብርሃን ጭምር ነው፡፡

የሥነ-ራዕይ ጥበብ (art of cinema, motion picture,film movie,kino) በሥልጣኔ ዕድገት ቅብብሎሽ መሠረታዊ ዕቅድ ውስጥ እንደ የዕይታ ቋንቋ ጥበብነቱ፤ የሚያገለግላቸውን ህዝቦች ‹‹የሥነ-ምግባር›› እና ‹‹የክብረ-ህሊና›› ብልፅግና ወይም የዝቅጠትን እንቅስቃሴ በማመላከት የቅርስ ማስቀመጫ የታሪክ ማህደር በመሆኑ ዘመናዊ እና ጥብቅ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡

እነዚህ ተቃቃፊ የኪነ-ጥበብ ጥብቆች ሥነ-ምግባር እና ክብረ-ህሊና፤ ከማህበረሰቡ ባህል የሚመነጩ፤ በአኗኗር ሂደት ውስጥ የሚዳብሩ ነዋሪ የዕውቀት ምግባራት ናቸው፡፡ በመንፈሱ የተጋ ፤ ክብረ-ህሊናው (Moral) የበለፀገ ህዝብ፤ የሀገሩን ዜጎች እና ምጣኔ ሀብት ዕድገት ተጨባጭ በሆነ ዕውነታ ማረጋገጡ ብሎም ለመጪ ዘመናት ተከታዮቹ በቅንነት ለመቀበል ቁርጠኝነቱ የማያሻማ ይሆናል፡፡ ለመልክዓ ምድር ተፈጥሮ፤ ለሥርዐተ ሰማይ ያለው ፍቅር እና ለሕዝቦች ያለው ክብር አይናወጥም፡፡

ሥነ-ምግባር (Ethics) ብለን ስንጠቅስም ግንባታው ከህዝቡ እሴታዊ አመለካከቶች ሥርዐት ከፍላጎቶቻቸው እና ከምቾቶቻቸው ይዘት ከሰዎች አድራጎት ማህበራዊ ደንቦች፤ ልማዶች፣ እና ባህሎች ጋር ከሚጣጣምበት ደረጃ እና የደህንነት ስሜት ነው፡፡

ለሥነ-ራዕይ ጥበብ ምንጭነት መሠረታዊ የዕድገት ሥነ-ምግባር መርሆች በባህላችን፣ የዕውነታ ኑረት ለማንነታችን መገለጫ፣ ለሥራ ትጋታችን፣ ለስንፍናችን፣ ለጋራ አሠራራችን፣ ለግንኙነታችን ፣ ለነፃነት አርበኝነታችን፣ ለፍቅራችን፣ ለሰብአዊነታችን እና ለዕምነቶቻችን ዓላማ በክብር እና በጥንቃቄ መቆም ናቸው፡፡ ክብረ-ታሪክን፤ ሩህሩህነትን፣ ፍትህን፣ ብሩህ ተስፋን ወ...እና የዓለም አቀፋዊነት ሥነ-ምግባር እሴቶችን ያቅፋል፡፡

ይህ በሆነበት ሁኔታ በአዲስ አበባ ይበልጡን የሥነ-ራዕይ ጥበብ ሥራ ምርት ምንም ያህል ከፍ ቢል እና የሚያስደንቅ ቢመስልም እንኳ የአዲሱ ህብረተሰብ የጥበብ አመንጪነት ችሎታ ብቸኛ መለኪያ ሊሆን እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡ ይሁንናም ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በሥነ-ራዕይ ጥበብ ሥራ በአርበኝነት የቆነጃጁ የሀገሪቱ ወጣቶች እና ጀማሪ ደቀመዛሙርት የምርቱ ሥራ ሂደት ባለቤቶች፤ የትረካው ፀሐፊዎች፣ የምሥል ቀረፃ፣ የመብራት፣ የድምፅ እና የዜማ ሥራ ባለሟሎች፤ የሥነ-ጥበብ ተጠሪዎች፤ የገፅ ቅብ ጠበብቶች፤ የአልባሳት ሥራ ሞያተኞች፤ የምስል አቀናባሪዎች፤ የእይታ ንድፍ ሠሪዎች፤ እና የምስለ-ተውላጥ (Animation) አቀናጂዎች ተዋንያን እና የምርት ሥራው ተባባሪዎች ወ... በሥራዎቻቸው የምልልስ ባህል ላይ ከእነሱ በተሞክሮ በእጅጉ ርቀው የሚገኙትን፤ አውሮፓ፣ እስያ እና አሜሪካንን በጣልቃነት እና በባህል ቅኝነት ሳያስቡ በራሳቸው ምጥቀት እና በሀገራቸው ቁመና ልክ የሥነ-ምግባር ግዴታዎቻቸውን እንዴት ይመለከቱታል?ይህ አመለካከት በኢትዮጵያ የሥነ-ራዕይ ጥበብ ታሪክ 2ኛው 50ኛ ዓመት በምንገኝበት በዚህ ዘመን የሥነ-ራዕይ ጥበብ መንግሥታዊ ተቋም በአገሪቱ ውስጥ የለም፡፡

የዕድገታቸው ልኬት እና አገራዊ ውጤቶቻቸው ሙሉ ዝርዝር በተሟላ መልኩ በቀላሉ ሊታይ ቢያዳግትም ሌሎች የኪነ-ጥበብ ዘርፎች በዘመናዊ መልኩ እና በኢትዮጵያ መንግሥት መቋቋማቸው ይታወቃል፡፡ ለመጥቀስም አለ የሥነ- ጥበብ ት/ቤት- 1950 .ም፤ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት- 1962 .ም እና ዮፍታሄ ንጉሤ የተውኔት ት/ቤት-1970 .ም ናቸው።

የትርዒት መድረክ እንቅስቃሴ እና የዳንኪራ ጥበብ በታወቁት ዐራት የአዲስ አበባ መንግሥታዊ ቴአትር ቤቶች ውስጥ እና በወታደራዊ ክፍሎች ለመድረኮቻቸው ትርዒት ጠቀሜታ እንደ ሥልጠና ሆኖ ከመከናወኑ ሌላ በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ፍላጎቱ ለነበራቸው ወጣቶች በሙያው ከፍተኛ ማዕረግ ባላቸው የውጭ አገር መምህር እስከ ባሌት ዳንኪራ ጥበብ ድረስ ትምህርቱ ይሰጥ እንደነበር ከማስታወስ በስተቀር በጥበቡ መንግሥታዊ ተቋም የለም፡፡

በሥነ-ራዕይ ጥበብ ዘርፍ በአዋጅ ቁጥር 306 1979 .ም በእልህ አስጨራሽ ጥናት ተፈቅዶ ተቋቁሞ የነበረው እና እጅግ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ‹‹የኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽን ›› በአዋጅ ቁጥር 151/1991 .ም ፈርሶ እንዳልነበር ሲደረግ የቪዲዮሎጂ ጥበብ ማሠልጠኛ ት/ቤቶች በግል የንግድ ፈቃድ ደንብ ተቋቁመው በተለየ መልኩ ከ1980ዎቹ መጨረሻ እስከ 2000 .ም አጋማሽ በአዲስ አበባ እና በናዝሬት/አዳማ በተከፈቱ ት/ቤቶች ውስጥ በፍላጎታቸው አጋጣሚ በቪዲዮግራፊ ትምህርት የተሳተፉ እና በሌሎች የሙያ ዘርፎች ከዲፕሎም እስከ ዶክትሬት ዲግሪ የትምህርት ማዕረግ የነበራቸውን ኢትዮጵያውያን ሳይዘነጉ የሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ጥቂት ተማሪዎችም የሶማሊያ፣ የጅቡቲ፣ የናይጄሪያ እና የኬንያ ይማሩ እንደነበር ሲታወስ ለምስለ-ቅርጽ (photograph) ጀምሮ የሥነ-ራዕይ ጥበብ ሥርዐተ ዕውቀቶች ላይ ይቀርቡ የነበሩ ሰፊ የመላምት እና የትግበራ ውጤቶች ሀተታዎች እና መዘርዝሮች በርካቶች እንደነበሩ ይታመናል።

15ሺህዎች በላይ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች እና ጎልማሶች በ12 ወራት የሥልጠና ጊዜ ያደረጉት በነበረው እረፍት የለሽ ትጋት የአገራቸው ኪነ-ጥብብ የሚመራባቸውን የማህበራዊ ሥነ-ምግባር መርሆች በሁሉም የኑሮ ዘርፎች ብርቱ ለውጦችን መታደግ የድርሻቸው ሂደት ላይ እንደሚገኝ በመረዳታቸው ነው። ለህብረተሰብ ደህንነት የሚካሄደውን ግልጽ ሥራ የክብረ ህሊና ዋጋ ቁንጮ አድርገው እንደሚመለከቱትም በሚሞክሩአቸው እና በዕቅድ በሚመላለሱባቸው የክየና ሥራዎቻቸው ልምዶቻቸው እና ውድድሮቻቸው ለአገራዊ ጉዳዮች መጣር እና ብቁ ሆኖ መገኘት ማለት እንደሆነ ማሰባቸውን እገነዘባለሁ።

በአንፃሩም በቀበሌ፣ በወረዳ፣ በክፍለ-ከተማ ብሎም በየክልላዊ መንግሥታት የባህል ጽ/ቤቶች እና መስተዳድሮች ትኩረት እና ድጋፍ በአብዛኛው እንደሚጎድለው በሚታይበት ሁኔታ በመጤ የባህል ውቃጭ ሳቢያ በአገረ-ሰብ ባህል እና ልማድ ጥበባዊ ሥራ እና ለግብ የሚታትር ዕውቀት በብርቱ እንደሚፈተን አይካድም።

ለኪነ-ጥበብ የሥነ-ምግባር ብቃት ውጤቶች አገማገም በዘመኑ ፈሊጥ ‹‹ማህበራት›› ተብዬዎችም ውስጥ በጋራ የጥበብ ሥራ ከጎንዮሽ ግንኙነቶች ጋር የማጠናከር አይደለም። የአምድዮሽ ግንኙነቶች ላይ እንኳ አበሳ ተደንቅሮ ይገኛል።

ወጣት ሴቶች በሥነ-ራዕይ ጥበብ ተሳትፎ ንቃታቸው እና በክብረ-ህሊናቸው ብቃት ላይ ሊረማመዱ የሚቀባቡ የዘማዊነት አንጎራጓሪ ቃለ ዝናዎች የሚያወግዝ ደንብ እና የስምምነት ቅፅ እስኪመስል እንደሚስተዋል በየቪዲዮሎጂ ማሠልጠኛ ተቋማት በግልጽ እና በዝርዝር እየቀረበ በውይይት ሲታይ እንደኖረ ይታወቃል። የኪነ-ጥበብ ደሀ ባልሆነች እና የሰው ጥበብን ማፍለቅ፤ የቅድስና መንፈስ በረከት መሆኑ በተረክ ሲፃፍ በባህልም ሲነገር በኖረባት አገር ኢትዮጵያ «እንኳ ገድል...» እንዲሉ የሚስተዋለውን የሴ...(የሴሰኝነት የሱሰኝነት የሙሰኝነት) ንጋሴ በክህደት በዋሾነት፣ በምቀኝነት እብጠት የገዘፈ መስሎ ቢታይም እንኳ በዚህም መሆን ባልነበረበት እና በማይገባው የተጎዱ እና የተሰናከሉ ይኖራሉ።

የምናባዊ ጽሑፍ አመንጪነት ዝንባሌ ያሏቸው ውስኖች «የቪዲዮሎጂ» ኪነ-ጥበባዊ ሥርዐትን በመመርመር የዕይታ ንድፍ በምስለ-ተውላጥ እና በማያ ቅንጅት ዕውቀቶች የጨመቱ ወጣቶች የሚፍለቀለቁበት ብሎም በተንቀሳቃሽ ሥዕል ቋንቋ ከመንግሥት የባህል ዕድገት ተጠሪ የሥነ-ራዕይ ዘርፍ በሌለበት እና ምንም ድጋፍ ሳይደረግላቸው በትወና ጥበብ ሥነ-አካላዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ብቃት ተፈጥሮ የተካኑ ሊደነቁ እና ሊያስገርሙ የሚችሉ የኢትዮጵያ ወጣቶችን ክብረ-ህሊና ከፍ ያረጉ ዕድለኞችን ለማስተዋል ያጋጠሙኝ ዓመታት አሉበት፡፡

ዛሬ በእርግጥ ሁሉም በአገራቸው እና በውጭ አገራት በየዕጣ ፋንታቸው መሰማራታቸው አልቀረም። የዛሬም የኢትዮጵያ የሥነ-ራዕይ ጥበብ የቪዲዮሎጂ ዕይታ መነሻ ውጤት በመሆኑ የእነዚህ ወጣቶች ትጋት ለሁላችንም ክብር እንደሚሰጥ ሁሉ፤ ወጣቶቹ የኢትዮጵያ የቪዲዮሎጂ ጥበብ ሥርዐት መነሻ የሀገሪቱ የዘመናዊ ሥነ-ራዕይ ጥበብ ትምህርት ታሪክ ምልክቶች መሆናቸውን አስባለሁ፡፡

በትምህርት ክትትላቸው ትጋት እና በክብረ-ህሊናቸው ብቃት የትምህርት ቤቶቻቸው ኩራት የነበሩ ወጣቶች በርካቶች ነበሩ፡፡ ዛሬም ሞያቸው በጠራቸው ሥራዎች ሁሉ በሥነ-ምግባራቸው ብቃት የሥራ ኃላፊነታቸውን ሥነ-ውበታዊ ዋጋውን ጠብቀው እና ክብረ-ህሊናቸው ተጠብቀው ሲተጉ አስተውላለሁ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በዚህች የታሪክ አገር ኢትዮጵያ የሥነ-ራዕይ ጥበብ ምርት ሥራ አገራዊ መርህ ዓቀፍ ደንብ (Film policy) እና የሥነ-ራዕይ መንግሥታዊ ተቋም በሌለበት ማህበረሰብ ውስጥ ወይም በዘርፉ የወጣቶችን ክብረ-ህሊና የሚያጎለብት የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ ልከኛ የዕውቀት ማቅረቢያ መንግሥታዊ ማሰናጃ በማይታይበት አገራዊ ውጤቶች ይፋጠናሉ ማለት አይታሰብም፡፡

ማዝገማቸውንም እንኳ ከልብ ፈቅዶ ለመቀበል ነዋሪ የሆኑትን የባህል ዕድገት ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ ቢታሰብ በዘመናችንም ከኪነ-ጥበብ ዘርፎች ለእኛ እጅግ አስፈላጊው የሥነ-ራዕይ ጥበብ በመሆኑ ባልተሟላ ሥርዐተ-ዕውቀት ወደፊት ይስተካከላል። ከምንም እንጀምር የሚባልበት ክፍለ ዘመን ላይ አለመሆናችንን አጥብቀን በመረዳት በየከተሞቻችን የሚታዩትን የቪዲዮሎጂ ጥበብ ሽርሽሮች በማስተዋል ከፍተኛ የሥነ-ራዕይ ጥበብ ተቋም ብለን ብቻ በሰብዓዊ ክብረ-ህሊና ላይ የኪሳራ ሥነ-ምግባር እና በጥበቡ የሥነ-ውበት ዋጋ ላይ ኃላፊነት የጎደለው ምልክት ማኖር የለብንም፡፡

የሥነ-ራዕይ ጥበብ (ለቪዲዮ ሥራ) የአስፈላጊ መሣሪያዎች አደረጃጀት ብቃት ያለው መንግሥታዊ ትምህርት ቤት በሙያ ዘርፍ አቀራረብ አቅም ከቦታ ይዞታ እና ከሰዎች አመራረጥ በሥነ-ራዕይ አመራር፣ በሥነ-ራዕይ ምስለ ቀረፃ፣ በስነ-ራዕይ ትወና ወ... የሚዘልቀው የተሳታፊዎች ሁሉ ክብረ-ህሊና ብሔራዊ ደረጃነቱ እንዲረጋገጥ ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ አሁን በሚታየው ደረጃ ይህንን ለመከወን ኢትዮጵያ አቅም እና ባለሙያዎች አሏት፡፡

በሥርዐተ ዕውቀቶች ልኬት የሥነ-ራዕይ ጥበብ እንደሌሎቹ የኪነ-ጥበብ ዘርፎች ዓለም አቀፋዊ ባህሪያት ያሉት በመሆኑ «ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ» እንዲሉ ሆኖ ጥቂት ግለሰቦችን በንዋይ እና በድርጎ ከማሟሟቅ በስተቀር በአገሪቱ ውስጥ በቪዲዮ ጥበብ ብቻ ተብሎ 2ኛ ክብረ-ጥናት (Degree) ወይም ከዚያ በላይ ተሰጥቷቸዋል ቢባል ከዘመናችን ፈሊጥ ጋር ከመዘባበቻነት ያለፈ ታሪካዊ ዋጋ በሚኖረው ቅርሳዊ መዳረሻ በሥነ-ራዕይ ንቃታዊ ተሳትፎ ይኖራቸዋል ማለት ያስቸግራል፡፡

ወጣቶች አእምሮአቸው እስከዘለቀበት ድረስ በነፃነታቸው እና በፍልስፍናቸው ተጉዘው በሥነ-ጽሑፍ፣ በግጥም፣ በሙዚቃ፣ በሥነ-ጥበብ እና በተውኔት እያቀረቡ እንዳሉት ሁሉ በሥነ-ራዕይ ጥበብ ሥራ በሚነሳሳው ክብረ-ህሊናቸው ግን ቅድመ ምርመራ ከሚመስለው አሠራር ተላቀው በከፍታ ክህሎታቸውን የሚያሳዩበት የምርምር መነሻ ሀሳባቸውን የሚያቃኑበት አእምሮአቸው እስከ ዘለቀበት ድረስ ተንሳፈው የሰብዓዊነታቸውን ፍልስፍና በዚህ በተደራሽነቱ ወደር በማይገኝለት የተንቀሳቃሽ ሥዕሎች ቋንቋ ምትሀት ለአገር፤ ለአህጉር እና ለዓለም የሚያቀርቡበት መነሻ ትምህርት ቤት በመንግሥት አጋፋሪነት ተቋቁሞ ገበታውም አስተማማኝ ከሆነ በኋላ ከምስክር ወረቀት ወደ ክብረ-ጥናት (Diploma) በመቀጠልም ወደ 1ኛ ክብረ ጥናት ወዘተ...

በሥነ-ራዕይ ጥበብ የመጎልመሻ ተቋም እና ነፃ የሆነ የትምህርት ዕድል መሠረቱ በማይታይበት ሁኔታ በአጋጣሚ እና በስልት የፈረንጅኛ ቋንቋ (እንግሊዝኛ) መምህራን ፈረንጆችን የሥነ-ራዕይ ጥበብ ምሁራን ናቸው ተብለው ለጥቅማቸው ብቻ አስመጥተን የመንጎራደዳቸው ክስተቶች ቢፈጠሩ እንጂ ለኢትዮጵያ ወጣቶች በሥነ-ራዕይ የሥነ-ምግባር እና የክብረ-ህሊና ጥማቸውን በመወጣት እርካታ ያስገኝላቸዋል ማለት ዘበትነቱ ከቃል በላይ የሚከብድ አይሆንም፡፡

የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት አመራረቅን እንደ አብነት ልብ ይሏል፡፡ ትምህርት ቤቱ በሚያስፈልጉት መሣሪያዎች በትክክለኛ የጥበቡ ዘርፎች መምህራን ብቃት ተሟልቶ በወቅቱ ዘመናዊ የመማሪያ ክፍሎች እና የትርዒት ማቅረቢያ አዳራሽ እንከን በማይወጣለት ሁኔታ ከተሟላ በኋላ ‹‹ብሔራዊ የሙዚቃ ት/ቤት›› ተብሎ ሁለት ዓመት በክህሎታቸው እና በፍላጎታቸው ተመዝነው በገቡ ተማሪዎች ልምምድ ከቆየ በኋላ ውጤታቸው እንደሚሰምር ታምኖበት ‹‹ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት››ተብሎ ይፋ ሲደረግ በልምምድ ላይ የነበሩት ተማሪዎች እና ከእነሱም በኋላ የአራት ዓመት ትምህርታቸውን እያጠናቀቁ በጠቅላላ ክብረ-ጥናት (General Diplom) እየተመረቁ ትምህርት ቤቱም የተጓዘበት ርቀት ይታወቃል፡፡ እንዲሁም ለአብነት ጠቅሼ በኢትዮጵያ ዛሬ ስለሌለው መንግሥታዊ የሥነ-ራዕይ ጥበብ ትምህርት ቤት ስጽፍ፤ በኢትዮጵያ ተዟዙሬ እንዳየሁት በወጣት ሴቶች እና ወንዶች የሥነ-ራዕይ ጥበብ የመነሳሳት ቀልብ ውስጥ አሁን በመፈጠር ላይ ያለው ሁኔታ ብርቱ ስሜት ሊያሳድሩ የሚችሉ የማህበረሰባቸው የቀድሞ ታሪክ እሴቶች እና የዘመናቸው አሻራ ትንግርቶች በዕውቀት ብቁ የሆኑ የአሠራር ቅርሶችን የመሻቱ ተግባር መጠኑ ከግምት በላይ ሀቅ በመሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም የተረካቢው ትውልድ ህልውና የበለጠ ትርጉም ባለው ማህበራዊ እና አገራዊ ጠቀሜታ የዳበረ እና በምጣኔ ሀብቱም ብሩህ ተስፋ የሚታይበት እንዲሆን የሥነ-ራዕይ ጥበብ ሥራ መንግሥታዊ ትምህርት ቤት መቋቋም እና መደራጀት አለበት፡፡

‹‹ብሔራዊ የሥነ-ራዕይ ጥበብ ሥራ ድርጅት›› እና በዚያም ሰንሰለት በተሟሉ የጥበቡ ሥርዐተ ዕውቀቶች እና የሙያ ዘርፎች የተዘጋጁ አካለ-ጥናት (Faculites) የተዋቀሩበት ከፍተኛ መካነ ጥናት (collage) በተጨባጭ መፈጠር አለበት! ›› የሚለው የዚህ ዘመን ዋነኛ ጥያቄ ከዘመናዊ ደንቆሮ መሰልነት የተነሳ‹‹ከቅዠት ያለፈ አይደለም›› ሊባል አይገባውም፡፡

ምናልባት ሁሉም ነገር የሚከናወነው እንደገመቱት ምሁራን እንደሚጠብቁት አይሆን ይሆናል፡፡ ይሁን እና ሁሉም ባስቸኳይ ያለትዕግሥት የጥበባዊ መላምቶቹን በይድረስ ይድረስ ወደጎን ባለመተው እና ስሜተኛነትን በማራቅ በዕውቀት የተከናወነ ይሆናል፡፡

ላለፉት አስራ ዘጠኝ ዓመታት በግል የንግድ ፈቃድ እና ደንብ መሠረት ከላይ እንደተገለጠው በቪዲዮሎጂ እና በሥነ-ጥበብ ማሠልጠኛ ተቋማት ታይቶ የነበረው የሥልጠና እይታ የወጣቶችን እና በፍላጎት የሚማሩትን ጎልማሶች ብቻ ሳይሆን የዚህ የሥነ-ራዕይ ጥበብ የቪዲዮ ምርት የትግበራ ሂደት የማህበረሰቡን የዕለት ተዕለት አስተውሎቶች አበረታቷል፡፡

በዚህ ጥበብ እንቅስቃሴ የዚህ ትውልድ ክብረ-ህሊና በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የመልሶ ማደራጀቱን ተግባር መደገፉን በመግለጥ ብቻ ሳይወሰን የአሁኑ እና የመጪው ዘመን አቢይ ተግባር ሆኖ እንደሚቀበልም አሳይቷል፡፡

የምስለ-ቅርጽ (Television) እና የቪዲዮ ጥበብ የሕዝብ ሥራ እና ኑሮ አመራሮች ሥራ ማስፈጸሚያ ወይም ስብከተ ድጋፍ እና የንግድ ድለላ ትርዒት ሽያጭ ማስተላለፊያ ብቻ እና ብቻ አለመሆኑን መገንዘብ ብቻም ሳይሆን ያለፈውን መንቀፍ የመሥራት ምልክት ሊሆን ስለማይችልም በጎደለው ሠርቶ ማሟላት እና ነገን ከዛሬ እና ከትላንት የተሻለ አድርጎ ለመቅረፅ ለሚተጋ ዘመናዊ ሕዝብ የህልውናው ባህሪያት ልማድ እና ቋንቋ የሚታዩበት ባህረ መዝገብ ማኖር እንደሆነ እና የታሪክን ጉዞ የሚያስቀምጥ ማህደር ጭምር እንደሆነ ተቀብለውታል፡፡

በእያንዳንዳቸው ተቋማትም ሁሉም ማለት በሚቻል መመዘኛ ያለማጋነን ተማሪዎች የየራሳቸው የሆነ ዋነኛ ተግባር ነበራቸው፡፡ በቪዲዮ ሥራ መሪነት ፣ በምስል ቀራጭነት፣ በቪዲዮ አቀናባሪነት እና በትወና ክፍሎች በፈጣን ክህሎታቸው ለመትጋት ተመላልሰውባቸዋል፡፡

ዕውቀት ያላቸው እና ይበልጥ በብቃት የሰለጠኑ ሠራተኞች ለመሆን ትጋታቸውን በተጨባጭ አሳይተዋል፡፡ በተሰማሩባቸው ቦታዎች ሁሉ እየተጉ መታየታቸውም የሁሉም የክብረ-ህሊናቸው አይነተኛ ዋጋ ትምህርት ቤታቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡

 

ብርሃኑ ሽብሩ የሥነ-ራዕይ ሥ..

Published in ማህበራዊ

ኢትዮጵያ ከበርካታ ዓመታት የድህነት፣ የኋላ ቀርነትና የሠላም እጦት ተላቅቃ፤ ዛሬ ላይ ህዝቦቿ በከፈሉት መስዋዕትነት የልማት ጎዳናን ጀምራለች፤ ህዝቦቿ የሠላም አየር መተንፈስ ጀምረዋል፡፡ ሆኖም ይህ የኢትዮጵያ አዲስ የድል ጉዞ የማይመቻቸው የፀረ ሠላም ኃይሎች ሰላሟን ለማደፍረስ፣ ህዝቦቿን ለማጋጨት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ይህ ሂደታቸው ግን በኢትዮጵያውያንና በልጆቻቸው የፀጥታ ኃይሎች የጋራ ጥምረት በየጊዜው ሲከሽፍ ታይቷል፡፡ ከእነዚህ የፀጥታ ኃይሎች ደግሞ የኢፌዴሪ የፌዴራል ፖሊስ አንዱ ነው፡፡ ለመሆኑ የፌዴራል ፖሊስ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አክብሮ ከማስከበር አኳያ ምን እየሠራ ነው? በሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከሆኑት ረዳት ኮሚሽነር ሓኔታ ገብረመድህን ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ፖሊስነት ለእርሶ ምንድን ነው?

ረዳት ኮሚሽነር ሓኔታ ፡- ፖሊስ የሚለው ትልቅ ትርጉምና ሰፊ ቢሆንም፤ ባጭሩ ለእኔ ፖሊስ ማለት ሠላም ማለት ነው፤ ፖሊስ ማለት ዴሞክራሲ ማለት ነው፤ ፖሊስ ማለት ፍትህ ነው፤ ፖሊስ ማለት ሕገ-መንግሥትና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን አክብሮ የሚሄድ የህዝብ አለኝታ ነው ብዬ ነው የምወስደው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የፖሊስ ተልዕኮ ሕገ- መንግሥታዊ ሥርዓቱን አክብሮ ማስከበር ነው የሚለው በምን መልኩ የሚገለፅ ነው?

ረዳት ኮሚሽነር ሓኔታ ፡- የፖሊስ ዋናው ተልዕኮ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መጠበቅ ነው፡፡ ይሄ የሚገለፅበት መንገድም በዋናነት ወንጀልን መከላከል እና ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝም መርምሮ በህግ አግባብ ፍትህ እንዲሰፍን ማስቻል ነው፡፡ ወንጀልን መከላከል ሲባል ግን ብቻውን የሚከላከልበት ሁኔታ አይደለም የሚኖረው፡፡ ከህዝብ ጋር ህዝብን ማዕከል እና መሰረት አድርጎ የሚያከናውነው ተግባር ነው፡፡ ዋነኛ ተልዕኮውም ወንጀልን በመከላከልና ወንጀልን በመመርመር የህዝብን ሠላምና ፍትህ ማስፈን እንደመሆኑ ከህዝብ ውጪ የሚሠራ ሥራ የለም፡፡

በዚህ መልኩ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ሲያስከብር፤ ፍትህ እንዲሰፍን ሲሠራና ለህዝበች ሠላም ሲደክም ቅድሚያ በራሱ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አክብሮ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ ምንግሥታዊ ሥርዓቱን አክብሮ በማስከበር ረገድ በዚህ መልኩ የሚገለጽ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የኢፌዴሪ የፌዴራል ፖሊስ ህብረ ብሔራዊ ነው ሲባል ምን ማለት ነው? እርሰዎስ በዚህ ላይ ያለዎት ዕይታ እንዴት ይገለፃል?

ረዳት ኮሚሽነር ሓኔታ፡- ሕብረ ብሔራዊነት የሚለው ኢትዮጵያ ወስጥ ያሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ የሚኖሩባት፣ የጋራችን ናት ብለው የሚያምኑባት አገር መሰረት አድርገው የሚንቀሳቀሱበት መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የፌዴራል ፖሊስን ትንሿ ኢትዮጵያ ብለን መግለፅ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ፌዴራል ፖሊስ ተዋፅዖን ማዕከል ያደረገ ተቋም ነው፡፡ የፌዴራል ፖሊስ እንደ ስሙ የፌዴራል ሕግና ሥርዓትን የሚያከብር እንደመሆኑ መጠን የሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተዋጽዖ ያለበት፤ ሁሉም የሚሳተፍበት ተቋም ነው፡፡ ስለዚህ በፌዴራል ፖሊስ የየትኛውንም የኢትዮጵያ ሰው (ብሄር ብሔረሰብ) ታገኛለህ፡፡ የየትኛውንም የኢትዮጵያ ክልል ታገኘዋለህ፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ስልን የፌዴራል ፖሊስ ማለት እንችላለን፡፡ ተግባሩም ስብጥሩም ይሄንን ነው የሚያሳየው፡፡

እዚህ ላይ መያዝ ያለበት ዋናው ነገር ሕብረ ብሔራዊነቱን ስንገልጽ ስብስቡ አይደለም፡፡ ስብስቡ አንድ መገለጫ ሊሆን ይችላል፡፡ ከስብስቡ በላይ ግን መሰረታዊ ይዘቱ እና ተልዕኮውን ነው የምናየው፡፡ ይሄ ሥርዓቱን መሰረት አድርጎ የተቋቋመ እና ሕገ መንግሥቱንና ሥርዓቱን የሚያከብር እንደመሆኑም መጠን፤ ሕገ መንግሥቱ የህዝቦች ሕገ መንግሥት እና የህዝቦች ሥርዓት ነው፣ በህዝቦች መፈቃቀድ የተመሰረተችው አዲሲቷ ኢትዮጵያም የምትመራበት ሕገ መንግሥት ነው፤ ተቋሙም ይሄንን ሕገ መንግሥት ተግባራዊ ለማድረግ የሚችልና የሚያስፈጽም መሆኑን፤ እና ይሄ ተቋም ደግሞ ከሁሉም ህዝቦች የተውጣጡ የፖሊስ አባላትን ያቀፈ እንደመሆኑ ሕብረ ብሔራዊነቱ በዚህ መልክ የሚገለፅ ነው፡፡ ስለዚህ የፌዴራል ፖሊስ በስብስብም ሆነ በተልዕኮ አፈፃፀሙ ሕብረብሔራዊነቱን የጠበቀ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከህብረ ብሄራዊነት አኳያ የፌዴራል ፖሊስ ስብጥር ሲታይ በትግል ወቅት ከነበሩ ድርጅቶች ጋር በተያያዘ በተለይ በአመራር ቦታዎች ላይ የቁጥር መብዛት እንደሚስተዋል ይነገራል፡፡ እርሰዎ ይሄን እንዴት ይገልፁታል? ይሄን ገጽታ ከመቀየር አኳያ ምን እየተሠራ ነው?

ረዳት ኮሚሽነር ሓኔታ ፡- በመሰረቱ የፌዴራል ፖሊስ የሙያ ተቋም ነው፡፡ የሙያ ተቋም ሲባል ደግሞ ማዕከሉ ፕሮፌሽናሊዝም ነው የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አሁን ባለው ሥርዓት ግን ሙያነት ብቻውን አይገልፀውም፡፡ ምክንያቱም ፖሊስነት ሙያ እና ሙያዊ ተቋም እንደመሆኑ ያለፉት ሥርዓቶችም ፖሊስ ነበራቸው፡፡ እንደየ አካባቢው ሊለያይ ቢችልም፤ በየትኛውም ዓለምና በየትኛውም ሥርዓት የሚኖር ሙያ ነው፡፡ ሙያው ሊዳብርና ሊያድግ፣ ከዘመኑም ጋር የሚሄድ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ ባለፈና ከሙያው በላይ ግን ከሥርዓቱ የመነጨው ማንነቱና ሕብረ ብሔራዊነቱ ወሳኝ ነው፡፡ በዛም መሰረት የተዋቀረ ነው፡፡

አዲስ ሥርዓት የተቋቋመ እንደመሆኑ ፌዴራል ፖሊስም በአመለካከቱ፣ በአስተሳሰቡና በሚከተለው ሥርዓትም አዲስ ተቋም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ አንፃር ሕብረ ብሔራዊነቱ በምልመላም ሆነ በቅጥር ሥርዓቱ ሁሉም እኩል በሆነ መንገድ (በኮታ) ነው የሚሳተፈው፡፡ ለዚህም መመዘኛ መስፈርቶች አሉ፡፡ አንዱ የመግቢያ በር ተዋጽዖን መሰረት ያደረገ ሕብረ ብሔራዊነትን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ቀጥሎ የተለያዩ ትምህርቶችና ሥልጠናዎች ሲሰጡም ይሄን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በየደረጃው ሁሉም ስብጥር አለበት፡፡ ከኮሚሽነር ጄኔራሉ ጀምሮ እስከታች ያለው ከሁሉም አካላት ያካተተ ነው፡፡

ከትግል ጋር ብናየው በትግል ያለፈ ብዙ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ዓለም፡፡ ግን ለታገለ ብቻ ተብሎ የተቀመጠ ቦታ የለም፡፡ እንደ ብቃቱ፣ እንደሙያው፣ እንደ ተዋጽዖው ነው፡፡ እርግጥ ነው ታሪካዊ አመጣጡ የራሱ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል፡፡ ምክንያቱም ሙያ እንደመሆኑ መጠን በአንድ ሌሊት የሚመጣ ሙያ የለም፡፡ በልምድ፣ በሥልጠናና በብዙ ውጣ ውረዶች የሚመጣ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ሙያና በዚህ መንገድ ያለፈው ብቁ ሆኖ የተገኘው ወደቦታው የመምጣት ዕድሉ በጣም ሰፊና ክፍት ነው፡፡ ክፍት የውድድር መመዘኛዎች አሉ፤ ዕገሌ ከዕገሌ ሳይባል እነዚህን መስፈትሮች የሚያሟላ ከሆነ ያልፋል፡፡ ከዚህ አንፃር ፌዴራል ፖሊስ በየደረጃው የተለያዩ እርከኖች ላይ ሁሉንም አካላት ያመጣጠነ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በሰው ብዛት ስብጥር ስናይም (ለምሳሌ፣ ክልል ከክልል ስናነፃፅር) የአማራ ክልል በጣም ይበዛል፡፡ ቀጥሎ የኦሮሚያ ይበዛል፡፡ ስለዚህ በዚህ ላይ ትግሉ የፈጠረው ተጽዕኖ የለም ማለት ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የፌዴራል ፖሊስ ሕብረ ብሔራዊነት ህዝቡ ውስጥ ገብቶ ከመሥራትና ተልዕኮውን ከመፈፀም አኳያ ለሚያከናውነው ተግባር ምን አስተዋጽዖ አለው?

ረዳት ኮሚሽነር ሓኔታ ፡- ሕብረ ብሔራዊነቱ የህዝብን ፍላጎትና ሠላም ከማስፈን አንፃር ፋይዳው ትልቅ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ውጤት ነው፡፡ ፌዴራል ፖሊስም በእነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች መሀል አብሮ የሚኖር፣ አብሮ ወንጀልን የሚከላከልና ፀጥታን የሚያስከብር አካል ነው፡፡ ተልዕኮውን ሲፈጽምም ከተነሳበት ዓላማ ነው የሚመነጨው፡፡ መመዘኛዎቹም ሕዝባዊነቱ እና የሕገ መንግሥት ጠበቃ መሆኑ ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን የፌዴራል ፖሊስ ከህዝብ የወጣ እንደመሆኑ አመለካከቱ ሕዝባዊ ነው፡፡ ስለዚህ በማንኛውም ቦታ እና አካባቢ ቋንቋና ባህል ሳይገድበው ሁሉንም በዕኩል የሚያገለግልበትና ለሁሉም በዕኩል ፀጥታውን የሚያስከብርበት፣ ተልዕኮውንም የሚፈጽምበት ነው፡፡

በየትኛውም አካባቢ ብንሄድ ሕዝቡ ለፌዴራል ፖሊስ ያለው አመለካከት በጣም ትልቅ ነው፡፡ ህዝቡ በተግባርም የሚያቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የሚከፍልበት አጋጣሚ በጣም ሰፊ ነው፡፡ የህዝቡን ችግር ለመፍታት ሌት ተቀን ላይ ታች የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ፋይዳውንም ከዚህ አንፃር ስናየው በጣም ትልቅና በየትኛውም ብሄር ብሔረሰብ ውስጥ ገብቶ ከህዝቡ ጋር እንዲሠራና ከህዝቡ ጋር በመሆንም ተልዕኮውን በብቃት እንዲወጣ ዕድል የሰጠው ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርሰዎም እንደገለፁት ወንጀልን ከመከላከል አኳያ የህዝቡ አጋርነት ወሳኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ታዲያ በፌዴራል ፖሊስ ተልዕኮ አፈፃፀም ውስጥ የህዝቡ ተሳትፎና አጋርነት እንዴት ይገለፃል?

ረዳት ኮሚሽነር ሓኔታ ፡- የፌዴራል ፖሊስ ከተልዕኮው አኳያ ብዙ ነገር እየሠራ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ፣ ሽብርተኝነትን ከመከላከል አንፃር የሚሠራቸው ሥራዎች አሉ፡፡ አሸባሪዎች ሲያዙም የመመርመር ተልዕኮም አለው፡፡ ከዚህ በዘለለም ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን፣ ኮትሮባንድን እንዲሁም ህገ ወጥ ንግድን መከታተልና መቆጣጠር የተልዕኮው አንድ አካል ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ በጣም ሰፋፊ ሥራዎች ናቸው፡፡ ከክልል ፖሊስ ተልዕኮዎች በመለስም በህዝብ አካባቢና መሃል የሚፈጠሩ ችግሮችን የማረጋጋት ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮ አለው፡፡ እነዚህ ከወንጀል ጋር በተያያዘ ለፌዴራል ፍርድ ቤት በተሰጠው አግባብ ለፌዴራል ፖሊስም የተሰጡ ናቸው፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ለተልዕኮው ግንባር ቀደም ሆኖ ከፊት ቢቀመጥም በስተጀርባው ህዝብ አለ፡፡ ማንኛውንም ሥራ ከህዝብ ውጪ መሥራት አይቻልም፡፡ በተጨባጭም እያየነው ያለነው ይሄንን ነው፡፡ በማንኛውም የወንጀል እንቅስቃሴዎችን በመከላከል ሂደት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የህዝብ ተሳትፎ አለበት፡፡ ለምሳሌ፣ በማንኛውም የፀረ ኮትሮባንድም ሆነ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት በሚደረገው እንቅስቃሴ፤ እንዲሁም በየትኛወም የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም የልማት አውታሮች በሚደረጉ ጥበቃዎችና የመከላከል ሥራዎች የህዝቡ ተሳትፎ አለበት፡፡

ከዚህ የምንረዳውም አንደኛ ያለ ህዝብ ተሳትፎ የሚሠራ ነገር የለም የሚለው ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ሲሆን፤ ሁለተኛም የህዝብ ተሳትፎ የሚመጣውም ከፖሊስ ህዝባዊነትና ከተቋሙ ባህሪ የመነጨ መሆኑን ነው፡፡ ይሄንን ካለፉት ሥርዓቶች ማነፃፀር ይቻላል፡፡ የደርግ ሥርዓት ፖሊስ ነበረው፤ ሆኖም በፖሊስና በህዝቡ መካከል የነበረው ግንኙነት የሚታወቅና የቅርብ ትዝታ ነው፡፡ ህዝቡ የእኔ የሚለው ፖሊስ አይደለም የነበረው፡፡ በአንፃሩ የሚሸማቀቅበት፣ ሠላምን በማረጋገጥ ላይ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ የነበረበት ተቋም ነበረ፡፡ የአሁኑ ፖሊስ ህዝባዊ ነው፤ መገለጫውም የህዝብ ተሳትፎ ነው፡፡ ስለዚህ እስካሁን የተሠሩ ሥራዎች ሁሉ በቀጥታም በተዘዋዋሪም የህዝብ ተሳትፎ አለበት፡፡

አዲስ ዘመን፡- የህዝቡ ተሳትፎ እንዲጎለብት የፖሊስ ህዝባዊነት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልፀውልኛል፡፡ የፌዴራል ፖሊስን ህዝባዊነት በምን መልኩ ነው መግለፅ የምንችለው?

ረዳት ኮሚሽነር ሓኔታ፡- የፖሊስ ህዝባዊነት መገለጫው ከመጀመሪያ ጀምሮ ፖሊስነት ለመቀጠር ሲመለመል አንዱ መለኪያው ነው፡፡ ፖሊስነት ማንም ዘው ብሎ የሚገባበት ተቋም አይደለም፡፡ የመጀመሪያው መመዘኛ ማንነት ነው፡፡ ማንነት ማለት ደግሞ የግለሰቡ ባህሪዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ግን በሥልጠና የሚሰጡና ህዝብን እንዲያከብር፣ እንዲያምንና እንዲያፈቅር የሚያደርጉ የሚሠሩ ሥራዎችና ሥልጠናዎች አሉ፡፡

ከፖሊስ እሴቶች አንዱ የህዝብን የበላይነት መቀበልና ማክበር ነው፡፡ በማንኛውም ጊዜና በማንኛውም እንቅስቃሴ የህዝብ የበላይነት መከበር አለበት፡፡ እኔ የህዝብ አገልጋይ ነኝ የሚል አስተሳሰብ እንዲይዝ፣ ተገልጋይ ሳይሆን አገልጋይነቱን አምኖ እንዲሄድ የሚያደርግ ነው፡፡ ስለዚህ ቅኝቱ በዚህ የሚመራ ነው፡፡ በመሆኑም ከላይ እስከታች ባለው በፖሊስ ውስጥ በተግባሩ ብቻ ሳይሆን በዕድገቱም ህዝባዊነት አንዱ መመዘኛው ነው፡፡ ሕዝባዊነት ለብቻው ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ ይህ ህዝባዊነትም ሕገ መንግሥቱን እና ከሕገ መንግሥቱ የወጡ ህጎችና ደንቦችን ከማክበር ጋርም የሚያያዝ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ፖሊስነት ታላቅ መስዋዕትነትን ይጠይቃል፤ ህዝባዊ ወገንተኝነትንም ይፈልጋል፤ በላቀ ስነምግባር ታንፆ በማንኛውም ሰዓት ለግዳጅ መዘጋጀትንም ይጠይቃል፤ በዚህ ረገድ በዘርፉ ያለው መልካም ተሞክሮ ምንድን ነው?

ረዳት ኮሚሽነር ሓኔታ ፡- በነገራችን ላይ ፖሊስ ለመሆን የመጀመሪያው መስፈርት ሕዝባዊነቱና ሕገ መንግሥቱን አምኖ ሕገ ምንግሥቱን አከብራለሁ፤ የህግን የበላይነት አረጋግጣለሁ ተብሎ ነው የሚገባበት፡፡ እንደገለጽከውም ፖሊስነት ሕይወትን የሚያስከፍል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በተለያየ መልኩ ህዝባዊ ባህሪውን ሊገልፁ የሚችሉ ከላብ ጠብታ ጀምሮ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የሚከፈልባቸው ሂደቶችና ውጣ ውረዶች አሉ፡፡ ፖሊስ ፀጥታን የማስከበር ተልዕኮ ያለበት እንደመሆኑም፤ ሌት ተቀን ህዝብን የሚያገለግልበትና የሚጠብቅበት ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎችና ቦታዎች (ከጠረፍ እስከ መሃል) ፖሊስ አለ ማለት ይቻላል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታና አገሪቱ ካለችበት የጂኦ-ፖለቲካል (የመልክዓምድራዊ ፖለቲካ አቀማመጥ) አኳያ ሲታይ፤ እነ አልሸባብና ሻዕቢያ በቀጣናው በመኖራቸው ለአሸባሪዎችና ለፀረ ሠላም ኃይሎች የተጋለጠ አካባቢ ነው፡፡ የፖሊስ በእነዚህ አካባቢዎች መኖር ደግሞ የህይወትን መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ሥራ እየሠራና በተጨባጭም ህይወቱን እንዲከፍል እያደረገው ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ በ2008 .ም በአገራችን ተከስቶ በነበረው የፀጥታ መደፍረስ ባጋጠመበት ወቅት ለማረጋጋት በተለያዩ ቦታዎች ዋጋ የከፈሉ ፖሊሶች ጥቂት አልነበሩም፡፡ ይህ ደግሞ ከተልዕኳቸው የመነጨ ነው፡፡ ምክንያቱም ጥቂት ፀረ ሠላም ኃይሎች በፈጠሩት ሁከት ፊት የሚመጣውን ንፁህ ህዝብ፣ ወጣቱን እና ሌላውንም የማያውቀውን የህብረተሰብ ክፍል ተኩሰው ላለመግደል ሲሉ መሳሪያ ይዘው በጦር ተወግተው ጭምር መስዋዕትነት የከፈሉ አሉ፡፡ ይሄም ፖሊስ ምን ያክል በጠበቀ ስነ ምግባር እየተመራ፤ ከራሱ ሕይወት ህዝብን በማስቀደምና ለህዝብ በማሰብ መስዋዕት እየከፈለ ህዝባዊነቱን በተግባር እያረጋገጠ መሄዱን የሚያሳይ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በዚህ መልኩ በግዳጅም ሆነ በማንኛውም አጋጣሚ በሥራ ላይ እያሉ ለሚሰው የፌዴራል ፖሊስ አባላት ቤተሰቦች ምን የሚደረግ ድጋፍ አለ?

ረዳት ኮሚሽነር ሓኔታ ፡- ፖሊስ መሆን ለህዝብ ህይወትን ለመክፈል ዝግጁ መሆን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ፖሊስ መሆን አለብኝ ብሎ ሲወስን መስዋዕትነት እንዳለ አምኖ የሚገባ ነው የሚሆነው፡፡ በየጊዜው በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችና ውጣ ውረዶች የሕይወት መስዋዕትነት ይከፍላል፡፡ አንድ ፖሊስ ደግሞ መስዋዕትነት ስለከፈለ ተብሎ የተለየ የሚደረግለት ነገር የለም፡፡ ግን ደግሞ ደንባችን አንድ ነገር ያስቀምጣል፤ የህይወት መስዋዕትነት የከፈለ የፖሊስ አባል ቤተሰብ (ሚስት፣ ልጆች፣ እናትና አባት) ይኖሩታል፡፡ ስለዚህ ተቋሙ በሚችለው መንገድ እነዚህን የመንከባከብና እገዛ የማድረግ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል፡፡

ከተቋሙ ደንብ አንፃር ስናይ መስዋዕትነት ለከፈለ የፖሊስ አባል ቤተሰቦቹ የአንድ ዓመት ሙሉ ደመወዙን እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ የጡረታ መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖም፤ የልጆቹና የባለቤቱ ነፃ ህክምና መብቶችም ህጉ በሚያስቀምጠው መሰረት አለ፡፡ በሥራ ላይ እያለ በህመም ምክንያት መስዋዕት ለሚከፍል ደግሞ ለቤተሰቦቹ የስድስት ወር ደመወዙን እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ይሄ ትልቅ ስለሆነ አይደለም፤ ሕይወት ለገበረ ከዛ በላይ ቢኬድ ተቋሙም፣ መንግሥታችንም ቅር የሚለው አይደለም፤ የሚያምንበትም ነገር ነው፡፡ ግን ከአገሪቱ አቅምና ይዞታ አንፃር ከዛ በላይ መሄድ ስለማይቻል ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከላይ ከገለፁት ባለፈ በአገር ውስጥ በሚፈጠሩ ቀውሶችን ከመከላከልና ከማርገብ አኳያ የአባላቱ ዲሲፕሊንና የግዳጅ አፈፃፀም እንዴት ይገለፃል? በጥንካሬ ከሚነሱ ጉዳዮች ባሻገር በድክመት ወይም በክፍተት የሚገለፁ ጉዳዮች አይጠፉምና እነዚህንም ቢገልፁልኝ? ችግሮቹን ለመፍታትስ ምን እየተሠራ ነው?

ረዳት ኮሚሽነር ሓኔታ ፡-የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ ሕገ መንግሥትና ሥርዓት ተጠቃሚ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድረበት ሕገ መንግሥታዊ መብት አግኝቷል፤ እንደድሮው አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የሚባል ማህበረሰብም የለም፡፡ ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ በትግሉ ያመጣው መብት ነው፡፡ ሆኖም መንግሥት ሊፈታቸው የሚገባው ከዕድገቱ ጋር ተያይዘው ዛሬም ድረስ በየጊዜው የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ እነዚህም ከመልካም አስተዳደር፣ ከሠላም፣ ከልማት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እነዚህን መንግሥት ለመፍታት የሚሄድባቸው ርቀቶች እንዳሉ ሆነው፤ በአንፃሩ በ2008 እና 2009 .ም ያየነው የእነዚህን ጥያቄዎች አቅጣጫ በማንሳትና በመቀየር የፀረ ሠላም ኃይሎች ወደ ሁከትና ብጥብጥ፣ ሥርዓቱን ወደማፍረስ የሄዱበት እንቅስቃሴ እንደነበር ይታወቃል፡፡

እነዚህን እንቅስቃሴዎች ፖሊስ በደንብ ያውቃቸዋል፡፡ ከሥልጠናው ጀምሮም የተገነዘባቸው ናቸው፡፡ በዚህም ፖሊስ በአንድ በኩል የህዝቡን ጥያቄ መመለስ ያለበትና ጥያቄውም ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን ስለሚያምን ይሄንን አክብሮ የሚሄድ ነው፡፡ የህዝቡን ጥያቄ ጠምዝዘው ለራሳቸው ፍላጎት ማሳኪያ ለማዋል የሚረባረቡ ፀረ ሠላም ኃይሎችን እንቅስቃሴም በሌላ መልኩ ነው የሚያየው፡፡ ስለዚህ ሁለቱም የተለያዩ መሆናቸውን ስለሚያውቅ እንደየአመጣጣቸው ነው የሚያስተናግ ዳቸው፡፡

የህዝብን ጥያቄ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ፣ ሕገ መንግሥቱ በሚጠይቀው ሥርዓት እስከሄደ በአግባቡ ማስተናገድ ብቻ ሳይሆን፤ ችግሩ እንዲፈታም የራሱን አስተዋጽዖ ያደርጋል፡፡ በተጨባጭም ይሄን አድርጓል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማመስ የሚረባረቡ ኃይሎችን በጠንካራ ፖሊሳዊ ስነ ምግባር ለመፍታት የሚያደርጋቸው ጥረቶችና እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡ ቅድም እንደገለፅኩት መስዋዕትነት የከፈለበት ሂደት ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ ምክንያቱም ታጥቆ የመጣን ጠላት ፊት ለፊት ትዋጋዋለህ፤ በህዝብ ተሸፍኖ የመጣን ጠላት ግን ህዝብን እየገደሉ ማጥፋት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ለአንድ ጠላት ተብሎ በርካታ ንፁሃንን ከሚፈጅ ራሱን መስዋዕት አድርጎ ህዝብን የማዳን እርምጃው ከህዝባዊነቱ ባለፈ የጥብቅ ስነ ምግባሩ ውጤት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሚያኮራ ታሪክ እየሠራ ያለ ፖሊስ ነው፡፡

ይህ ውጤታማ ተግባሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን፤ እዚህም እዚያም የሚንጠባጠቡ ክፍተቶች ይኖራሉ፡፡ ከስነ ምግባር(ዲሲፕሊን) ጋር ተያይዞ የሚነሱ ክፍተቶች አሉ፡፡ ከማህበራዊ ሚዲያው ጋር በተያያዘና በሌሎች ምክንቶችም አልፎ አልፎም የሚታዩ ሕገ መንግሥትን የማፍረስ አመለካከትና አስተሳሰቦች ሰለባ የመሆን ነገሮች ይታያሉ፡፡

እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላትና ችግሮቹንም ለመፍታት የሚያርምበት፣ የሚገነባበትና የሚያስተካክልበት ተቋማዊ አሠራር አለ፡፡ ትልቁ የሚከተለው አቅጣጫም ፖሊስ ሁልጊዜም ከወቅቱ ጋር የሚራመድ አስተሳሰብና አመለካከት እንዲይዝ በተለያየ መንገድ የአቅም ግንባታ ሥራዎች የማካሄድ ነው፡፡ በየዕለቱ በሠላም ሠራዊት ግንባታ ላይ የመጀመሪያ ሥራው አድርጎ ስለሚሠራም ብዙ ችግሮች እየተፈቱ ነው፡፡ ከዚህ ወጥቶ ጫፍ የሄደ ካለም በአሠራር ደንቡ መሰረት ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ይወሰዳሉ፡፡ ለምሳሌ፣ የዲሲፕሊን ግድፈት የሚፈጥሩና ሕዝባዊ አስተሳሰብን ወደጎን ትተው ወደራሳቸው የሚያተኩሩ አልፎ አልፎ ይታያሉ፡፡ በግለሰብ ደረጃ ቢሆንም የጠላት ሰለባ የመሆን ዕድልም ያጋጥማል፡፡

ስለዚህ አልፎ አልፎ የሚታዩ የዲስፕሊን ጉድለቶችና ክፍተቶች በማንኛውም አካል ሊኖርና ሊታይ እንደሚችል ሆኖ፤ ግን ደግሞ ከተልዕኳችን አንፃር በቸልተኝነት የሚታለፍ አይደለም፡፡ በጣም ትኩረት የሚፈልግና ትልቅ ግምትም የሚሰጠው እንደመሆኑ፤ በእነዚህ አካላት ከተቋም ከማባረር ጀምሮ በህግ እስከ መጠየቅ ቁርጠኛ እርምጃ ነው የምንወስድ፡፡ ችግሩን ለመፍታትም ከላይ እስከታች ያለው አመራርና አባል የሚረባረብበት ስለሆነ፤ እስካሁን የከፋ ችግር አለ ማለት አይቻልም፡፡ ከተልዕኮውና ከሚሰጠው የቤት ሥራ አንፃርም የሚሠሩ የግንባታ ሥራዎች ስላሉም ለወደፊቱም አይኖርም፡፡

ሌላው እንደክፍተት ሊታይ የሚችለው ከአቅምና ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ ሲሆን፤ አንድ ፖሊስ ፖሊስነትም ሆነ ተቋሙ የሚፈልገውን ሙያዊ ብቃት፣ አስተሳሰብና አመለካከት ሊኖረው፤ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንም ሊታጠቅ ይገባዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይሄ ከአገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተያይዞ የሚታይ እንደመሆኑ መጠን ደረጃ በደረጃ የሚፈታ እንጂ በአንድ ጊዜ ይፈታል ማለት አይደለም፡፡ እየተፈቱ ያሉ ነገሮች አሉ፡፡ አቅም በፈቀደም ችግሮቹን ለመፍታት የሚኬድባቸው ርቀቶች ብዙ ስለሆኑ የጎላ ችግር አለ ማለት አይቻልም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ወንጀልን ቀድሞ ከመከላከልም ሆነ ከተከሰቱ በኋላ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ከማድረግ አኳያ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በምን መልኩ እየሠራችሁ ነው?

ረዳት ኮሚሽነር ሓኔታ፡- ወንጀልን ከመከላከል አንፃር ከተለያዩ አካላት ጋር አብሮ ይሠራል፡፡ በተለይ ከልል የፀጥታ አካላት ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለው፡፡ ከደህንነትና መከላከያ ጋርም በተመሳሳይ፡፡ ከእነዚህና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የተሳሰረ የጋራ እቅድና እንቅስቃሴዎች አሉት፡፡ ለምሳሌ፣ ኮትሮባንድን ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ ፌዴራል ፖሊስ የራሱ ተልዕኮ ቢኖረውም ብቻውን የሚሠራው ሥራ የለም፡፡ ከገቢዎችና ጉሙሩክ ባለሥልጣን፣ ከማዕድን ሚኒስቴርና ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ጋር የሚያገናኝ እቅዶች አሉት፡፡

ወንጀልን እንዲሁም ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በአገር አቀፍ የተቋቋመ ግብረ ኃይል አለ፡፡ ኮትሮባንድን ለመከላከልም በአገር አቀፍ የተቋቋመ ግብረ ኃይል አለ፡፡ እነዚህ ግብረ ኃይሎች ከላይ ጀምሮ እስከታች ኮማንድ ፖስቶችና አደረጃጀቶች አሏቸው፡፡ በእነዚህ አደረጃጀቶች ፌዴራል ፖሊስ አለበት፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አስተዋጽዖ እያደረገም ይገኛል፡፡ ይሄም ከባለድርሻ አካላት የጠበቀ ቁርኝት እንዳለውና እየሠራቸው ያሉም ሆነ ለወደፊት በሚያከናውናቸው ሥራዎች ብቻውን እንዳልሆነ፤ የሌሎች አካላት አስተዋጽዖ እንዳለው ታሳቢ ሊደረግ እንደሚችል የሚያሳይ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የፌዴራል ፖሊስ ወንጀልን ከመከላከል አኳያ ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም(ኢንተርፖል) ጋር እየሠራ ይገኛል፡፡ ተቋሙ በአፍሪካ ያለውን ማዕከል አዲስ አበባ ከማድረጉ ጋር ተያይዞ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ከመከላከልና ወንጀለኞችንም አሳልፎ ከመለዋወጥ አንፃር የሚኖረው ፋይዳና የተገኙ ውጤቶች ምንድን ናቸው?

ረዳት ኮሚሽነር ሓኔታ፡- የፌዴራል ፖሊስ የኢንተርፖል አባል ነው፡፡ እንደ አባልነቱም የኢንተርፖል ህጎችንና ደንቦችን ያከብራል፡፡ በኢንተርፖል ስምምነት ውስጥ ተሳታፊ ሆኖ መብቱንም ግዴታውንም እየተወጣ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ከሁሉም የኢንተርፖል አባል አገራት ፖሊሶች ጥብቅ የሆነ ግንኙነት አለው፡፡ በተለይ ደግሞ ከምሥራቅ አፍሪካ ፖሊስ ኮሚሽኖች ጋር የጠበቀ ግንኙነትና በየዓመቱም የጋራ ጉባኤ ያካሂዳል፡፡ ስለዚህ በተስማሙበት መንገድ ወንጀለኞች ተላልፈው የመሰጠት እንቅስቃሴዎች በተግባር እየታየ ነው፡፡

በዚህ ስምምነት መሰረትም በቅርብ ጊዜ ከተለያዩ አገራት (ከሳዑዲ አረቢያና ከሌሎችም) ተላልፈው የተሰጡ ወንጀለኞች አሉ፡፡ በዚህም ወንጀለኛ በየትም አገር ሄዶ ማምለጥ እንደማይችል የሚያውቅበት፤ በተግባርም የተረጋገጠበት ደረጃ ነው ያለው፡፡ ከኢንተርፖል ጋር ያለው የጠበቀ ግንኙነትም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የአፍሪካ የኢንተርፖል ማዕከልም በአዲስ አበባ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ቢሮ ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህም ከኢንተርፖል ጋር ያለን ዝምድና የጠበቀና የቀረበ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን፤ በየጊዜው የመረጃ ልውውጥ በማድረግም አስፈላጊ ሥራዎች እየተሠሩ እንዳሉ የሚያሳይ ነው፡፡ ለቀጣይም በይበልጥ ተጠናክሮ የሚሄድ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የፌዴራል ፖሊስ የአገር ውስጥ ፀጥታና ሠላምን ከማስፈን ባለፈ በተለያዩ መድረኮች የሠላም ማስከበር ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ይሄ ሂደት እንዴት ይገለፃል? እንዲጠና ከርስ ምን እየተሠራ ነው?

ረዳት ኮሚሽነር ሓኔታ ፡-የፌዴራል ፖሊስ በአገር ውስጥ የሚያደርገውን የፀጥታ ማስከበር ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ዓለማቀፋዊ ተልዕኮውንም በመፈፀም ላይ በተወሰነ መልኩም ቢሆን የራሱን ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ ራሱን የቻለ ክፍል አቋቁሞም ይሄን በሚያግዝ መልኩ እየተከታተለና እየሠራ ይገኛል፡፡ ወደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት(ተመድ) የሚገባ ፖሊስ የሚወዳደረውም በምልመላና ፈተና እንደመሆኑም፤ አባላቱ እነዚህን ፈተናዎች ለማለፍ ብቁ እንዲሆኑ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ የራሱን አስተዋጽዖ እያደረገ ነው፡፡ በዚህ መልኩም የፌዴራል ፖሊስ ብቻ ሳይሆን የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖችም የፖሊስ አባሎቻቸውን እንዲያሳተፉ እየተደረገ ሲሆን፤ በዚህ ወርም በርካታ አባላት ፈተና ወስደው ከፌዴራልም ከክልልም ያለፉ አሉ፡፡ እነዚህም ለተልዕኮ ሲጠሩ የሚሰማሩ ይሆናል፡፡

ይህ ቀጣይነት ያለው የተልዕኮ ሂደት እንዳለ ሆኖ፤ አሁን ወደሌላ ተጨማሪ ተግባር ለመግባት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ይሄም የታጠቀ የፖሊስ አሃድ (ፎርምድ ፖሊስ ዩኒት/ ኤፍ../ የሚባለው) አደራጅቶ የማሰማራት ተልዕኮ ለመጀመር በእንቅስቃሴ ላይ ነው፡፡ ወደዛ ለመግባት የሚያስችል ሥራዎችም እየተሠሩ ናቸው፡፡ በተመድ በኩልም አወንታዊ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ በቅርብ ጊዜም መጥተው አይተዋል፡፡ የተመድ ተልዕኮ እየሰፋ የሚሄድ እንጂ የሚያቋርጥ ባለመሆኑ ይሄን ለማድረግ የሚያስችል መስመር ውስጥም እየገባን ነው፡፡

ይሄንን ማድረግ ሁለት ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ በአንድ በኩል ፖሊስ በተመድ ተልዕኮ ሂዶ በሚሠራቸው ሥራዎች የራሱን ማንነትና ስነ ምግባሩን እያንፀባረቀ ተልዕኮውን እየፈፀመ በሄደ ቁጥር በአገራችን የሚፈጠረው አወንታዊ ስዕል ቀላል አይሆንም፡፡ በመከላከያ ሠራዊታችን የምናሳየው ነገር አለ፡፡ በፖሊስም ተመሳሳይ አዎንታዊ የሆነ አመለካከትና ስዕል በተለይም ደግሞ ሠላም በሚያስከብርበት አካባቢ በአዎንታ ከመገንባት አንፃር ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ስለዚህ የአገራችንን ስዕል በአወንታ እንዲታይ በማድረግ እየተጫወቱ ያለውን አወንታዊ ሚና ለወደፊቱም በዛ መልኩ ነው የሚሄዱት፡፡

በተመድ ስር ኢትዮጵያ የፖሊስ ኃይሏን ማሰማራት ከጀመረች ስምንት ዓመታት የሆኑት ሲሆን፤ በየጊዜውም የተሳታፊ አባላት ቁጥር እያደገ አሁን ላይ በአንድ ጊዜ እስከ መቶ ሰው ለማሳተፍ የተቻለበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ እነዚህ ወደተለያዩ የተመድ ስምሪት ቦታዎች የሚሰማሩ ሲሆን፤ የእኛ ድርሻ ለዚህ ተልዕኮ ብቁ የሚሆን አባል ማዘጋጀት ነው፡፡ ይህ ሂደት በእኛ ላይ አዲስ ቢሆንም በሌሎች አገሮች የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ እንደ ሩዋንዳ ባሉ አገሮች ተመሳሳይ የኤፍ..ዩ አሃዶች አሏቸው፡፡ ስለዚህ እነርሱ ራሳቸውንም አገራቸውንም ከማስተዋወቅ አንፃር ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ እናም ይሄንን ተግባር ለመፈፀም የሚያስችል ሂደት እንዳለ ሆኖ፤ ስምሪት ግን እንደ ታዛቢ(ኦብዘርቨር) ተበታትኖ የሚሄድ አይሆንም፡፡ በአንድ ኮማንድ ስር ሆኖ የሚሄድ ነው የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ ሁለትና ሦስት ዩኒት ከሆኑ በሁለትና ሦስት ኮማንድ ስር ሆነው ነው የሚሄዱት፡፡ ስለዚህ የዚህ ዩኒት መሰማራት አንደኛ ከሌሎች ጋር ሆኖ ከሚያከናውነው ተግባር በተሻለ እንዲያከናውንና በሚያሳየው ውጤታማ ተግባርም የአገሪን ገፅታ ለመገንባት ያስችለዋል፡፡ ምክንያቱም አቅሙንም ሆነ ስነ ምግባሩን በተሻለ መልኩ ማሳየት ስለሚያስችለው ፖሊስም እንደ መከላከያ ሠራዊቱ ለአገር ገፅታ ግንባታ የላቀ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

ሁለተኛም እዛ የሚሄደው አባል ለራሱ የሚያገኘው ጥቅም አለ፡፡ እዚህ ያለው ደመወዝ እንደተጠበቀ ነው፡፡ ስለዚህ እዛ ሄዶ በሚያገኘው ጥቅም ለራሱና ለቤተሰቡ፤ ብሎም ለአገሪቷ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ እንደመኖሩ መጠን፤ ይሄንን ሂደት ቀጣይነት እንዲኖረው ይፈለጋል፡፡ በዛ መሰረትም ተቋማችን እየሠራ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻም ለፌዴራል ፖሊስ አባላትም ሆነ ለህብረተሰቡ እና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድን ነው?

ረዳት ኮሚሽነር ሓኔታ፡- ለፖሊስ የማስተላልፈው መልዕክት፣ ፖሊስ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማስከበር የሚያስችል ትጥቅ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይሄ ትጥቅ የአመለካከት ትጥቅ ነው የሚሆነው፡፡ በአመለካከት ሕገ መንግሥቱን ለማስከበር የሚያስችል ሰብዕና ሊኖረው ይገባል፡፡ ይሄንን ለማድረግም ዕውቀቱን በየጊዜው የማስፋትና ዘመኑ ከሚጠይቀው የወንጀል ስፋቶች አንፃር የሚመጣጠን አቅም ይዞ ለመሄድ ብዙ ሊሠራ ይገባል፡፡

ሕገ መንግሥቱን ማክበር ስንል ትልቁ መገለጫው፣ በአንድ በኩል ፖሊሳዊ ሰብዕናዎችን ማክበር፣ ማስከበርና ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ፖሊሳዊ ሙያዊ ዕውቀቱም በዛው መጠን መስፋት ይገባዋል፡፡ ከዛ በላይ ደግሞ ሕዝባዊ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ሕዝባዊ ሳይኮን ሕገ መንግሥትን መጠበቅ፤ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንም ማስከበር አይቻልም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ተያይዘው የሚሄዱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ፌዴራል ፖሊስ የብሔር ብሔረሰቦች ተምሳሌት እና ይሄንን የሚያንፀባርቅ ኃይል እንደመሆኑ መጠን፤ የየዕለት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችም ይሄንን በሚገልፅ መንገድ መሆን አለበት፡፡

ፖሊስ ሕገ መንግሥቱን የሚያከብረው እንዲሁ አይደለም፤ ህይወቱን በመክፈል ነው፡፡ አሁን ያለው የአገራችን ሁኔታ እንደምናውቀው በተለያየ መንገድ ይህችን አገር ሰላሟንም ሆኖ ሥርዓቱን ለማደፍረስ የውጭም የውስጥም ፀረ ሠላም ኃይሎች ርብርብ እያደረጉ ነው የሚገኙት፡፡ እነዚህን ኃይሎች ለመመከት የሚያስችል ትጥቅ ሊኖረው ይገባል፡፡ ለዚህም አንደኛ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሚገባ ማወቅ ይገባዋል፡፡ ፀረ ሠላም ኃይሎችንም ለመዋጋት የሚያስችል የአመለካከትና የአስተሳሰብ ትጥቅ ሊታጠቅ ይገባዋል፡፡ በሌላ በኩል አሁን ያለውን ሁኔታ ስናየው እነዚህ ኪራይ ሰብሳቢዎችና ፀረ ሠላም ኃይሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የህዝብን ጥያቄ ወዳላስፈላጊ አቅጣጫ እየመሩ ብጥብጥና ሁከቱ እንዲቀጥል የማድረግ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ መሰረታዊ መፍትሄው የፖለቲካ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ከፀጥታ ማስከበር አንፃር ግን ፖሊስ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከሌሎች የፀጥታ አካላት እንዲሁም ከህዝብ ጋር ሆኖ ለመመከት ሌት ተቀን መሥራት እንዳለበት መልዕክት ለማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡

ህዝቡም ይሄንን ሥርዓት ያመጣው በትግሉ ነው፡፡ መስዋዕትነት ከፍሎበታል፡፡ ይሄንን ሥርዓት የሚጠብቀው በዋናነት ራሱ ህብረተሰቡ ነው፡፡ ከህዝቡ በላይ ሌላ ኃይል የለም፡፡ ይሁን እንጂ ይሄንን ለማስፈፀም የሚያስችል የራሱ የሆኑ ልጆች በፀጥታ ጥበቃ ላይ አሰማርቷል፡፡ በፌዴራል ፖሊስም የእነዚህ ህዝቦች ልጅ ነው፡፡ ስለዚህ ሥርዓቱን ከመጠበቅ አንፃር እንደ በፊቱ ሁሉ አሁንም ከፖሊስ ጎን ሆኖ አሸባሪዎችንም ሆነ ፀረ ሠላም ኃይሎችን በመመከት ረገድ ሚናውን እንዲጫወት ለመጠየቅ እፈልጋለሁኝ፡፡

በሌላ በኩል አገራችን የጀመረችውን የልማት ጉዞ ለማኮላሸት እና የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለማስፈን የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን የምናየው ነው፡፡ ይሄ በኮትሮባንድ፣ በህገ ወጥ ንግድና በሌሎች የተለያዩ መንገዶች እየታየ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ለመመከት ህዝቡ ወሳኝ ሚና እንዳለው ታሳቢ በማድረግ ከፀጥታ ኃይሎቻችን ጎን እንዲሰለፍ በዚህ አጋጣሚ ለመጠየቅ እፈልጋለሁኝ፡፡ ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም እንደ እስካሁኑ እጅና ጓንት በመሆኑ ከፌዴራል ፖሊስ ተቋማችን ጋር ለጋራ ሥራና ተልዕኮ እጅና ጓንት ሆኖ የሚሠራው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ አመሰግናለሁ፡፡

ረዳት ኮሚሽነር ሓኔታ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

 

ወንድወሰን ሽመልስ

 

Published in ፖለቲካ

ከዛሬ አስር ዓመት በፊት በአንዲት አነስተኛ የብረታ ብረት ወርክ ሾፕ ነበር ኤን.ኤ ሜታል ኢንዱስትሪና ኢንጅነሪንግ ሥራውን የጀመረው፡፡ ኤን.ኤ ሜታል ኢንዱስትሪና ኢንጅነሪንግ ዛሬ የደረቅና የፈሳሽ ጭነት ማመላለሻ ተሳቢዎችንና የገልባጭ መኪና መለዋወጫ አካሎችን እንዲሁም መሬት ውስጥ የሚቀበሩ ታንከሮችን፣ የነዳጅ ማደያ ካኖፒዎችንና ዲፊውዘር ፕላንቶች በማምረት ምርቶቹን ለአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያም የሚያቀርብ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ሆኗል፡፡

ባሳለፈው ሳምንት ደግሞ ከኢትዮጵያ አልፎ በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የሲኖ ትራክ መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ አስመርቋል፡፡ ይህም በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ በሚገኘው የአገሪቱ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ እንዲሸጋገር የሚያግዝ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ባሻገርም ሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ይሆናል፡፡

የኤን.ኤ የፋብሪካው ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ነብዩ አሰፋ፣ የሲኖ ትራክ መገጣጠሚያ ፋብሪካውን መመረቅ አስመልክተው እንደተናገሩት፤ ኤን.ኤ ብታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ፋብሪካ ሥራ የጀመረው ከአስር ዓመታት በፊት እርሳቸውን ጨምሮ በጥቂት ሠራተኞች ብረት ነክ ምርቶችንና የነዳጅ ማደያ ታንከሮችን በማምረት ነበር፡፡ በብረታ ብረት ዘርፍ ተሰማርቶ እሴት እየጨመረ ምርቱን ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ገበያዎች ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ቀስ በቀስም ምርትና አገልግሎቱን እያስፋፋ የአሁኑን ግዙፍ የሲኖ ትራክ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለማስመረቅ በቅቷል፡፡

እንደ አቶ ነብዩ ማብራሪያ፤ ፋብሪካው ከተመሰረተበት 1999 .ም ጀምሮ ለምህንድስና ሥራ የሚሆኑ የብረት ውጤቶችን በማምረት በዓለም አቀፍ ግዥ፣ በፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ በነዳጅ መሸጫና ማደያ ግንባታ፣ ልዩ ልዩ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ጋኖችን በማቅረብ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ተቀባይነትን ማግኘት ችሏል፡፡ የገበያ ፍላጎትን በማጤንና ተገቢውን ምላሽ በመስጠትም ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ፋብሪካው ጣሊያናዊ አማካሪ በመቅጠር የከባድ ጭነት ተሳቢዎችን ማምረትና መሸጥን አዋጭነት በማስጠናት ተግባራዊ በማድረጉ አመርቂ ውጤት አስገኝቶለታል፡፡

በዚህም ከ2006 .ም ጀምሮ ከፍተኛ የደረቅና ፈሳሽ ጭነት ተሸካሚ ተሳቢዎችን ማምረት የጀመረ ሲሆን፤ ምርቶቹም በገበያው ላይ ተቀባይነትን አግኝተውለታል፡፡ በመሆኑም የፋብሪካው ምርቶች ለአገሪቷ የትራንስፖርት ኢንዱስትሪ እንዲሁም የነዳጅና ቅባት አከፋፋዮች አስተማማኝ መፍትሄዎች መሆናቸው የተረጋገጠበት ደረጃ ላይ ማድረስ ተችሏል፡፡ አሁንም ተጨማሪ የገበያ ዳሰሳ ጥናት በማካሄድና ከዋናው አምራች ኩባንያ (ከሲኖ ትራክ ኢንተርናሽናል) ጋር በመፈራረም የሲኖ ትራክ መኪናዎችን በአገር ውስጥ መገጣጠም የሚያስችል ፋብሪካ ማስመረቅ ችለዋል፡፡

ኤን.ኤ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪና ኢንጅነሪንግ አስካሁን ድረስ በተለያዩ ትልልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች ተሳትፎ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፤ በሥራዎቹም ጉልህ አስተዋፅኦዎችን አበርክቷል፡፡ ለአብነትም ከመከላከያና ብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ጋር በመተባበር ለኦሞ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት የዲፊውዘር ፕላንት ምርትና ተከላ ሥራን በብቃት አከናውኗል፡፡ ይህም ከአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚጠበቁ በመንግሥት የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ርብርብ ውስጥ ፋብሪካው የራሱን ድርሻ እየተወጣ ለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ነው ሥራ አስኪያጁ ያመለከቱት፡፡

ሥራ አስኪያጁ፣ የፋብሪካው ምርቶች ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካታቸው በዘርፉ የሚባክነውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከማዳናቸው ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካ ገበያም የሚላኩ በመሆናቸው ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ገቢም የሚያስገኙ መሆናቸውንም ይጠቁማሉ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖርም ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ፋብሪካው ምርትና አገልግሎቱን ለተጠቃሚ የሚያደርሰው ከአራት እስከ አምስት በሚደርሱና ተራርቀው በሚገኙ የኪራይ ቦታዎች መሆኑን ያስታወሱት አቶ ነብዩ፤ በአሁን ሰዓት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሊዝ ባገኙት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የማምረቻ ፋብሪካ ገንብተው ሥራቸውን እያከናወኑ መሆናቸው ገልፀዋል፡፡ ለዚህም የከተማ አስተዳደሩን በማመስገን፤ በገቡት ውል መሰረት ቦታውን ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ማዋላቸውን ተናግረዋል፡፡ ለፋብሪካው ግንባታም ሁለት መቶ ሃምሳ ሚሊዮን ብር ኢንቨስት ማድረጋቸውን፤ ለአራት መቶ ኢትዮጵያውያን ቋሚና ለአምስት የውጭ ዜጎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቁመዋል፡፡

የሲኖ ትራክ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ፕሬዚዳንት ሚስተር ዛሃንግ ዝሆንግ በበኩላቸው፤ ሲኖ ትራክ የተለያዩ የሲቪልና የጦር ተሸከርካሪዎችን በማምረትና በመሸጥ ሥራ ላይ የተሰማራ ዓለም አቀፍ የቻይና መኪና አምራች ድርጅት ገልዋል፡፡ ምርቶቹም ከአንድ መቶ በላይ በሚሆኑ የዓለም አገራት እንደሚሸጡ ተናግረዋል፡፡

እንደ ሚስተር ዛሃንግ ዝሆንግ ማብራሪያ፤ ቻይናና ኢትዮጵያ ካላቸው ሁሉን አቀፍ ትብብር አኳያ የሲኖ ትራክ መገጣጠሚያ ፋብሪካ በኢትዮጵያ መገንባቱም አገራቱ ተባብሮ ለማደግ ያላቸውን ጠንካራ ፍላጎት የሚያመላክትና ኢኮኖሚያዊ ትብብራቸውንም ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው፡፡ የሲኖ ትራክ ምርቶች ከዚህ ቀደምም በኢትዮጵያ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደመሆኑም፤ እንደ ኤን.ኤ ዓይነት የሲኖ ትራክ መገጣጠሚያ ምርቶችን በአገር ውስጥ የሚያመርት ፋብሪካ መምጣቱ ደግሞ የአገሪቱ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ እንዲያድግና ኢትዮጵያውያኑ ወደ ፊት የራሳቸውን የሲኖ ትራክ ምርቶች እንዲያመርቱ በር የሚከፍት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ የሲኖ ትራክና ኤን.ኤ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪና ኢንጅነሪንግ ትብብርና ሽርክናም ፋብሪካ በመገንባት ብቻ የሚያቆም ሳይሆን የጋራ ፍላጎትንና ዓላማን ለማሳካት ዘላቂነት ባለው መልኩ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጀማል ረዲ በበኩላቸው፤ በዕለቱ የተመረቀው የሲኖ ትራክ መገጣጠሚያ ፋብሪካና የትሬለር ማምረቻ ፋብሪካ የከተማ አስተዳደሩ የአምራች ኢንዱስትሪውን ለማስፋፋት የሚያደርገው ሰፊ እንቅስቃሴ ተግባራዊ ማሳያ እንደሆነ ነው የገለፁት፡፡ ይህም መንግሥት በአዲስ አበባና መሰል የአገሪ ትልልቅ ከተሞች በኢንጂነሪንግ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት የነደፈው አምራች ኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጅ እንደሆነ እና አገራዊ ፋይዳውም የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “መንግሥት የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ዘርፉን ለማሳደግ የነደፈውን ፖሊሲ ተከትሎ ከተሠራ በአስቸጋሪ ሁኔታዎችም ውስጥ ሆኖ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ኤን.ኤ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪና ኢንጅነሪንግ እየሠራ ያለው ሥራና እያስመዘገበው ያለው ውጤት ተጨባጭ ማሳያ ነው” ሲሉም ገልፀዋ፡፡

እንደ አቶ ጀማል ገለፃ፤ ተግባሩ ለብዙዎቹ የሥራና የተስፋ ምንጭ ሊሆን የሚችል ስለሆነ ሊበረታታ ይገባዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ዘርፉን ለመደገፍ እያደረገ ያለውን ጥረት የበለጠ በማጠናከር ከተማ አስተዳደሩም ሆነ በተለይ ደግሞ የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በዘርፉ ሊያመጣ የሚችለውን የቴክኖሎጅና የዕውቀት ሽግግር ስለሚገነዘብ ፋብሪካው የሚያበረታታና ሙሉ ድጋፍ የሚያደርግለት ይሆናል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚንስቴር ሚንስትር ዲኤታ አቶ ዓለሙ ስሜ በበኩላቸው፤ የፋብሪካው ባለቤት ወጣት መሆኑን አመላክተው “በወጣቱ ባለሀብት በአስር ዓመት ውስጥ የተከናወነው ስኬታማ ሥራ ለሌሎችም የአገራችን ወጣቶች አርዓያነት ያለው አኩሪ ተግባር ነው” ብለዋል፡፡ የተጀመረው የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በማረጋገጥ በኩል የአምራች ኢንዱስትሪው ሚና የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በተለይም የብረታ ብረትና የኢንጅነሪንግ ንዑስ ዘርፍ ለሌሎች አምራች ኢንዱስትሪዎች ዕድገትና ለቴክኖሎጅ ሽግግር ካለው ጠቀሜታ አንፃር የሚፈለገውን ያህል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ የሚደገፍና የሚሠራበት እንደሚሆንም ገልፀዋል፡፡

እንደ ሚንስትር ዴኤታው ገለፃ፤ የዚሁ ዘርፍ አንድ አካል የሆነው የሲኖ ትራክ ከባድ መኪና መገጣጠሚያና የትሬለር ማምረቻ ፋብሪካ በአገሪቱ መጀመሩ ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቀዱ መሳካትና ለቴክኖሎጅ ሽግግር ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህም በአሻገር አዲስ የተመረቀው ኤን.ኤ የሲኖ ትራክ መገጣጠሚያ ፋብሪካ አገሪቱ በ2017 .ም በአፍሪካ የቀላል አምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል ለመሆን የምታደርገውን ሁሉን አቀፍ ርብርብ የሚያግዝና የበኩሉን ድርሻ የሚወጣ በመሆኑ አገራዊ ፋይዳው የላቀ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም የፋብሪካውን የሥራ ሂደት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በቅርብ እየተከታተለ የሚደግፈው ይሆናል፡፡

መገጣጠሚያ አካላትን በመፈብረክ የሚጀምረው የፋብሪካው ሥራ ውሎ አድሮ እየጎለበተ እንደሚሄድና ሙሉውን መኪናውን እዚሁ በአገር ውስጥ ወደ ማምረት እንደሚሸጋገር ያላቸውን ዕምነት በመግለፅም፤ በቀጣይ ፋብሪካው በሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

 

ይበል ካሳ

Published in ኢኮኖሚ

የምዕራብ አፍሪካ አገራት ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ኢኮዋስ/ECOWAS) በሠላም አልባዋ ሊቢያ በአፍሪካውያን ህገ ወጥ ስደተኞች ላይ እየተፈጸመ ስላለው ኢሰብአዊ ጉዳይ ሰሙኑን መግለጫ አውጥቷል፡፡ ኮሚሽኑ በመግለጫው እንዳመለከተው፣ በዘመናዊው ዓለም ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመጡ ሕገ ወጥ ስደተኞች ወደ አውሮፓ አገራት ለመሄድ ሊቢያን ያቋርጣሉ፡፡ ሆኖም ሊቢያ ላይ አሰቃቂ ኢሰብአዊ ድርጊት ይፈጸምባቸዋል፡፡ አፍሪካውያን ህገ ወጥ ስደተኞች በተለይ ናይጀሪያውያን እንደ ባሪያ ይታያሉ፤ አገሪቱም ልታስተናግዳቸው አለመቻሏን ስደተኞበቹ ይናገራሉ፡፡

የምዕራብ አፍሪካ አገራት ኢኮኖሚ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ማርሴል አላይን ዲ ሳውዛ፣ ኮሚሽኑ በአቡጃ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት በሊቢያ ስላለው አሳሳቢ የስደተኞች አያያዝ ጉዳይ ተናግረዋል፡፡ የኮሚሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ኤድዋርድ ሲንጋቴይ በበኩላቸው፣ በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሊቢያ ላይ ያለው ያልተገባ የህገ ወጥ ስደተኞቹ አያያዝ በተለይ ከባሪያ ንግድ ጋር በተያያዘ የሚያጣራ የምርመራ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ኢኮዋስ፣ ስደተኞችን ለመታደግ አቅም ባይኖረውም ከዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ስደተኞቹን ለመታደግ

ቀጥታዊ ድጋፍ እያፈላለገ መሆኑም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል፡፡ በሊቢያ ላይ እየተፈጸመ ያለው ድርጊት በአሁኑ ጊዜ ተቀባይነት የሌለው መሆኑ በመጠቆም፤ በተለይ ከምዕራብ አፍሪካ አካባቢ የሄዱ ወጣቶች ስደተኛ ላይ በሊቢያ ምን ያክል ኢሰብአዊ አያያዝ እየተፈጸመባቸው እንዳለ በትክክል ለማወቅ አለመቻላቸውን አመልክተዋል፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቱ አክለውም፣ ሊቢያ በመሄድ ዜጎቹን ለማምጣት የሚያስችል በቂ የገንዘብ አቅርቦት እንደሌላቸው እና ለዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የአስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ደብዳቤ መላካቸውን አስታውቋል፡፡

የአፍሪካውያን ስደተኞች ግፍ በሊቢያ

በመቶዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ስደተኞች በአፍሪካዊት አገር ሊቢያ ምድር ላይ በየሳምንቱ ልክ እንደ ዕቃ በባሪያ ገበያ ይሸጣሉ፣ ይገዛሉ፡፡ በርካቶች ክፍያ እንዲፈጽሙ ታግተው ይገኛሉ፤ አልያም ለአጋቾቻቸውና ህገ ወጥ አዟዟሪዎቻቸው ገንዘብ ለመክፈል የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዲፈጽሙ እንደሚገደዱ የህገ ወጥ የሰዎች አዟዟሪዎች ለአልጀዚራ ተናግረዋል፡፡ ብዙዎቹ በአዟዟሪዎቹ በጠራራ ጸሐይ ተደብድበው፤ ወይም በውኃ ጥም ተቃጥለው፤ አልያም በመኪና አደጋ በሊቢያ በረሃ እንደሚሞቱ ሳልማን የተባለ የሰዎች አዘዋዋሪ ይናገራል፡፡

አብዛኞቹ የአፍሪካ ስደተኞች የሚመጡበት በደቡብ ሳብሃ ከተማ የምትገኘው ማረፊያ በሰው አስካሬን የተጨናነቀ ሲሆን፤ በአካባቢው ማቀዝቀዣ ባለመኖሩ ሁኔታው እንዲባባስ ማድረጉም አንዳንድ የሊቢያ የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ በአዟዟሪዎቹ ተገድለው በአካባቢው በጅምላ የተቀበሩ ሰዎችን አሰቃቂ ሁኔታ እንደሚመለከቱ እና የሟቾቹ ማንነት በደምብ ለማወቅም እንደማይቻልም ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡

ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን ያልጠቀሱት ባለሙያ እንደገለጹት፤ በሳብሃ ማረፊያ ጣቢያ በአግባቡ መስራት የማይችል አንድ ማቀዝቀዣ ሲኖር፤ የሞተ አካል ሳይበላሽ ሊቆይ የሚችለው በማቀዝቀዣው ለሦስት ቀናት ብቻ ሆኖ ሳለ በህገ ወጥ አዟዟሪዎቹ ግን ለወራትም ሲጠቀሙበት ተመልክተዋል፡፡

የአውሮፓ መግቢያ በር

እንደሚታወቀው ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚወጡ ስደተኞች አውሮፓ ለመግባት ብቸኛው አማራጭ የሊቢያን በረሃና ውቅያኖስን በማቋረጥ ጣሊያን መግባት ነው፡፡ አብዛኞቹ ስደተኖች ከጋና፣ ናይጀሪያ፣ ካሜሩን፣ ዛምቢያ፣ ሰኔጋል፣ ጋምቢያና ሱዳን የሚመጡ ሲሆን፤ ሊቢያ የሚደርሱትም በኔትወርክ ትስስር በተገናኙ አደገኛ ወንጀለኞች አውሮፓ እናድርሳችኋለን በሚለው ከእውነት የራቀ የማታለያ ዘዴ በመጠቀም መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሊቢያም ወደ አውሮፓ በባህር ለመሄድ የተመቸች ብቸኛዋ አገር ብትመስልም፤ ጉዞው ለስደተኞቹ እጅግ አደገኛ ከመሆኑ በላይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ150 ሺ በላይ ሰዎች ህይወት በባህር ላይ አልፏል፡፡

ከዚህም በላይ በስንት መከራ ሊቢያ የደረሱ ስደተኞቹ አስቸጋሪውን የባህር ጉዞ ሳይደርሱ በአፍሪካውያን ልጆች በአፍሪካዊቷ አገር አፍሪካውያኑ እንደ እቃ ይሸጣሉ፣ ይገዛሉ፣ ይገደላሉ፣ ብዙ መከራ ይቀበላሉ፡፡ በቅርቡ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ከምዕራብ አፍሪካ የመጡና በሳብሃ ግዛት በጋራዥና የመኪና ፓርክ አገልግሎት ለመስራት የተሸጡ ስደተኞች ማነጋገሩን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ድርጅቱ አንድ ሰኔጋላዊ ስደተኛ በመቶዎች ከሚቆጠሩ እንደሱ ያሉ ስደተኞች ጋር በሳብሃ በአንድ ግለሰብ ቤት እንደ ንብረት ተገዝተውና የቤቱ ንብረት ሆኖው እየኖሩ መሆናቸው እንዲሁም ድብደባ እንደሚርስባቸው፣ እንዲለቀቁ ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲልኩላቸው እንደሚገደዱም መናገራቸውን ገልጿል፡፡

ስደተኞቹ ከአንዱ ቤት ለማስለቀቅ ሌላ ሊቢያዊ ለባለቤቱ በአዲስ ዋጋ እንዲሸጥለት ይደረጋል፡፡ ከዛም በሌላ ሊቢያዊም ልክ እንደ እቃ ተገዝቶ ያለ አንዳች ክፍያ ያገለግላል፡፡ አንድ አንዶቹ ለአጋቾቻቸው መክፈል ያልቻሉ ወይም የሚገዛቸው ያጡ ይገደላሉ፤ አልያም በርሃብ ተሰቃይተው እንዲሞቱ የሚበላ የሚጠጣ በሌለበት ቦታ ይጥሏቿል፡፡ ስደተኞቹ ሲሞቱ ወይም ሲለቀቁ ሌሎች አዳዲስ ስደተኞች ደግሞ እነሱን ለመተካት ተገዝተው ይመጣሉ፡፡

በሙዓመር ጋዳፊ የሚመራ የነበረው የሊቢያ መንግሥት ከስልጣን ከተወገደ ወዲህ አገሪቱ ለአፍሪካውያን ስደተኞች እንዲሁም የአገሪቱ ሰላማዊ ነዋሪዎች መርገጫ የሌላት የመሬት ሲኦል ስትሆንባቸው፤ በአንጻሩ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚተዳደሩ ወንጀለኞች ግን የመሬት ገነት ሆናለች፡፡ ሳልማን የተባለው ህገ ወጥ የሰዎች አዟዟሪ በስልክ ከአልጀዚራ ጋር ባደረገው ቆይታ ያረጋገጠውም ይሄን ነበር፡፡ በኒጀር አካባቢ በአጋዴዝና ዚንደር ከተሞች ባሉ ቢሮዎች ስደተኞቹ ከህገ ወጥ ስደተኞቹ ጋር ትውውቅ እንደሚደረግላቸውም ሳልማን ጠቁመዋል፡፡

ለወሲብ ማስገደድ

የሰዎች አዟዟሪዎቹ በኒጀር ከሚገኙ አዛዦቻቸው ስደተኞቹን ለመውሰድ መልእክት ሲደርሳቸው ስደተኞቹን የማጓጓዝ ሂደት ይጀምራሉ፡፡ አዟዟሪዎቹ ከ735 እስከ 1100 ዶላር ከአንድ ሰው ይቀበላሉ፡፡ ክፍያውን ከተቀበሉ በአነስተኛ ፒክአፕ መኪኖች አጨናንቀው በመጫን በሊቢያ በረሃ (ሙቀቱ በክረምትም ቢሆን ከ50 ዲግሪ ሴንትግሬድ በላይ በሆነ) አልቃትሮን ከተባለች ስፍራ ወደ ሳብሃ ያደርሷቸዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ የኒጀር ኮማንደሮች ከሌሎች የአፍሪካ አገራት የተስማሙት ስምምነት መኖሩንም ሳልማን ይናገራል፡፡

መሐመድ ሐሰን የተባለ ሊቢያዊ እንደሚናገረው፤ በተለይ ሴቶች አጋዥ የሌላቸውና የት መሄድ እንዳለባቸው ባለማወቃቸው በሊቢያ ላይ ተጥለው ይቀራሉ፡፡

አልቃትሮን ከሳብሃ በ300 .ሜ ርቀት የምተገኝና የኒጀር አዋሳኝ ስትሆን በየዓመቱ፤ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞቹ ሊቢያ የሚገቡም በዚች ትንሽየ ከተማ ነው፡፡ ሳብሃ ከገቡ በኋላ ግን ስደተኞቹ በኮማንደሩ ቁጥጥር ስር ናቸው፡፡ መጠልያ፣ ምግብና ከለላ የመሳሰሉ አገልግሎቶች ወደ ሌላ አካል ወይም ወደ ሌላ የሰዎች አዘዋዋሪ ወይም የድለላ ኔትዎርክ ወይም ወደ ሌሎች በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የሚገኙ ኮማንደሮች እንደ ባሪያ ከመሸጣቸው በፊት የሚሰጣቸው ኮማንደሩ ነው፡፡

ስደተኞቹ ምንም ከለላ በሌለው ግልጽ መሬት አልያም በአነስተኛና ጽዳታቸው ባልጠበቀ ክፍሎች እንዲኖሩ ይገደዳሉ፡፡ ለግብረ ስጋ ግንኙነት የማስገደድ ተግባርም በከተማው በይበልጥ መስፋፋቱ ይነገራል፡፡ ለግብረ ስጋ ግንኙነት በከተማ ወንዶች ይሁኑ ሴቶች በ735 ዶላር ወይም አንድ ሺ የሊቢያ ዲናር ይቀርባሉ፡፡ የጋናና ካሜሩን ደግሞ ከዛ በላይም ሊሆን ይችላል፡፡

ሊቢያውያን አፍሪካውያን ስደተኞች እስካሉ ድረስ ምንም ችግር እንደሌላቸው ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ በሳብሃ የሚታየው ከጋና፣ ካሜሩን፣ ናይጀሪያና ዛምቢያ በቻድና ኒጀር አድርገው በሚመጡ ስደተኞች መጨናነቅ በመጥቀስ ይናገራሉ፡፡ መሐመድ ሐሰን የተባለው ሊቢያዊ፣ በዓይኑ ያየውና በማስረጃነት ድረገጹ የጠቀሰው አንድ ኮማንደር በአንድ ጊዜ አምስት ሴቶችን መሸጡንና ሴቶቹም ወዲያውኑ ለግብረ ስጋ ግንኙነት እንዲፈጽሙ መገደዳቸውን ጠቅሷል፡፡

አፍሪካውያን ስደተኛ ሴቶች በሊቢያ ናይት ክለቦች ለሚጠቀሙ በሴተኛ አዳሪነት እንዲያገለግሉ እንደሚደረጉም ማየታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በሀገሪቱ የሚገኙ በተለይ ሴቶቹ አጋዥ የሌላቸውና መሄጃ አጥተው ሊቢያ ላይ የሚቀሩ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ይህንን መሰል የማጣራት ተግባር አልጀዚራ የመረጃ አገልግሎት ብቻውን ሊወጣው እንደማይችል በመጥቀስ፤ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረታቸውን በሊቢያ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርጓል፡፡ ዘገባው ከዴይሊ ፖስትና አልጀዚራ የተጠናቀረ ነው፡፡

ለትውስታ ያክል!

ስለቀድሞው የሊብያ መሪ መዓመር ጋዳፊ መታወቅ ያለበት አስር ነጥቦች ብሎ ግሎባል ሪሰርች ድረ ገጽ እንደሚከተለው ጠቅሷል፡፡ ጽሑፉ እኤአ በ2014 ለንባብ የበቃ ሲሆን፤ አሁን ባለው ሁኔታ ሊቢያ ከነበራት ጠንካራ መንግሥት በአሜሪካና የተባበሩት የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር /ኔቶ/ ፍርክስክሷ በመውጣቷ ተከትሎ ስለቀድሞ መሪዋ መዓመር ጋዳፊ መታወቅ የሚገባቸው አስር ነጥቦች በድጋሜ ድረ ገጹ ይዞ ወቷል፡፡

1. በሊቢያ ቤት እንደ ተፈጥሯዊ የሰው መብት ይታያል፤

2. ትምህርትና የጤና አገልግሎት ለሁሉም ነፃ ነበር፤

3. ጋዳፊ የዓለም ግዙፉ የመስኖ ፕሮጀክት የነደፈ ነበር፤

4. የግብርና ቢዝነስ ለመጀመር የምትጠየቀው ክፍያ የለም /ነፃ ነበር/

5. ለአራሶች /ለወለዱ እናቶች/ የፋይናንስ ድጋፍ ይደረግላቸው ነበር፤

6. መብራት በነፃ ነበር፤

7. ነዳጅ በርካሽ ነበር፤

8. ጋዳፊ የትምህርት ደረጃ ከፍ እንዲል አድርጓል፤

9.ሊቢያ የራሷ አገራዊ ባንክ ነበራት፤

10. የሊቢያ ገንዘብ ከወርቅ የተሠራ ዲናር ነበር፤

በመጨረሻ ድረ ገጹ መዓመር ጋዳፊ ዕውነት አሸባሪ ነበር ወይ? ብሎ ይጠይቃል፡፡ ዕውነትም አሸባሪ አልነበረም አገሪቱ ግን ወደ ሽብር ገብታለች!!

 

በሪሁ ፍትዊ

Published in ዓለም አቀፍ

 

ኅዳር 29 ቀን 2010 .ም አስራ ሁለተኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የአፋር ብሔራዊ ክልል መንግሥት ርዕሰ መዲና በሆነችው ሠመራ ከተማ «በሕገ መንግሥታችን የደመቀ ሕብረ፣ ብሔራዊነታችን ለህዳሴያችን» በሚል መሪ መልዕክት ይከበራል። ይህ መሪ መልዕክት ሦስት ቁልፍ ጉዳዮችን ያካተተ ነው - ሕግ መንግሥት፣ ሕብረ፣ ብሔራዊነትና ህዳሴ። የዘንድሮውን መሪ መልዕክት ለማጣጣም እነዚህን እርስ በእርስ የተሳሰሩ ጉዳዮች በቅጡ መመልከት ይገባል።

ኅዳር 29 ቀን1987 .ም የፀደቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የአገሪቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነ ሕግ ነው። ኢትዮጵያ በመጪው ዘመን እደርስበታለሁ ብላ ላቀደችው ብልፅግና ያስቀመጠችው መሪ አቅጣጫም ተደርጎ ይወሰዳል። ለእዚህም ነው በሕገ መንግሥቱ መግቢያ «የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መጪው የጋራ ዕድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል፤ ጥቅማችንን፣ መብታችንና ነፃነታችንን በጋራ እና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን፤ በትግላችንና በከፈልነው መስዋዕትነት የተገኘውን ዴሞክራሲና ሠላም ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ፤ይህ ሕገ መንግሥት ከዚህ በላይ ለገለፅናቸው ዓላማዎችና ዕምነቶች ማሰሪያ እንዲሆነን እንዲወክሉን መርጠን በላክናቸው ተወካዮቻቸን አማካይነት አፅድቀነዋል» ሲሉ ቃል የገቡት።

ይህ በሕዝቦች ጥልቅ ውይይት የዳበረ እና የፀደቀ ሕገ መንግሥት የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የዘመናት የሠላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ጥያቄዎች መልሷል። ወደፊትም ለተያዘው አቅጣጫ ገዢ የሕግ ማዕቀፍ ሆኖ ይቀጥላል። በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ በሁሉም ዜጎች ልብ የሰረፀ የቃል ኪዳን ሰነድ እንዲሆን ግንዛቤ የመፍጠሩ ሥራ ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫ መሆን አለበት። በተለይም አገር ተረካቢ የሚባለው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል በውስጡ የተካተቱት አንቀጾች ምን አንደምታ እንዳላቸው በተገቢው መንገድ በመገንዘብ ለተያዘው የለውጥ ጉዞ መሰረት የሆነውን ሰነድ የማስከበር ሚናውን እንዲወጣ ኃላፊነት የተጣለባቸው አካላት የቤት ሥራቸውን መሥራት አለባቸው።

ሕብረ ብሔራዊነት የኢትዮጵያ መገለጫ ነው። ይህም በተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ብሔሮች እና አመለካከቶች ይንፀባረቃል። ይሁንና የቀድሞዋ ኢትዮጵያ ይህን ሕብረ፣ ብሔራዊ የሆነ ስብጥር ለዘመናት በአግባቡ ማስተናገድ አቅቷት ኖራለች። በዚህ የተነሳ መብታቸው ያልተከበረላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ከግዳጅ አንድነት ይልቅ በጦርነት የሚገኝ ነፃነትን መርጠው ወደ ትግል ተሰማርተው ነበር። በ1983 .ም በሁሉም የአገሪቱ ውድ ልጆች የህይወት መስዋዕትነት ከተገኘው ድል በኋላ የፀደቀው ሕግ መንግሥት የአመለካከትና የሃይማኖት ነፃነትን ከማስከበሩም በላይ ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብቱን እንደተጎናፀፈ ደንግጓል። ለሁሉም የአገሪቱ የሕብረተሰብ ክፍሎች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ዋስትናና ዕውቅና በመስጠት ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲመሰረት መሰረት ጥሏል።

የአገሪቱ ብዝሃነት ለዘመናት ከተነፈገው ዕውቅና ተላቆ በፅኑ መሰረት እንዲቆም ሕገ መንግሥቱ ቁልፍ ሚና አበርክቷል። ይህም መላው ሕብረተሰብ በሕገ መንግሥቱ ጥላ ስር በመሆን ሕብረ፣ ብሔራዊነቱ ያመጣው ልዩነት ሳያግደው ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ተከብረው የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እንዲታትር መሰረት ጥሎለታል። በእዚህም በአለፉት 26 ዓመታት በአገሪቱ ተጠቃሽ ዕድገት እንዲመዘገብ አቢይ ምክንያት ሆኗል፤ የህዳሴው ጉዞ ተጀምሯል።

በአገሪቱ በአለፉት ዓመታት በሠላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ተጨባጭ ለውጦች ቢገኙም እንዲሁ በቀላሉ የመጡ አልነበረም። በአገር ውስጥ ከሚፈጠሩት ችግሮች ባሻገር የውጭ ጥቃቶችና ተፅዕኖዎች ለውጡን ተገዳድረውታል። ይሁንና በተያዘው ትክክለኛ መስመርና በመላው ሕዝብ የላቀ ትብብር እየተመከቱ አሁን ለተገኘው ለውጥ ለመድረስ ተችሏል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሕብረ፣ ብሔራዊ አንድነታችን ባስገኘልን ትሩፋቶች ላይ የተቃጡ እክሎች መታየት ጀምረዋል።

የአንድነታችንና የህዳሴያችን ጉልበት የሆነው ሕብረ፣ ብሔራዊነታችንን እንደ ዋዛ ለመሸርሸር የሚደረጉት የጥፋት ኃይሎች ከንቱ ሙከራ በአብዛኛው ሠላም ወዳድ ሕዝብና ለውጡን በማጣጣም ላይ በሚገኘው ሕብረተሰብ በፅኑ እየተወገዘ መሰረት እንዳይኖረው ቢደረግም፤ አሁንም ከዚህም ከዚያም የሚታዩትን ግጭቶች ለማስቀረት የሕዝቦች የተባበረ ክንድ ያስፈልጋል። በተለይ አገር ተረካቢ ወጣቶች በልዩነት ውስጥ ያለውን የአንድነት አቅም ተገንዝበው የለውጥ መሣሪያ ሊያደርጉት ይገባል።

«በሕገ መንግሥታችን የደመቀ ሕብረ፣ ብሔራዊነታችን ለህዳሴያችን» ሲባል ልዩነት ውበት መሆኑን ከመቀበል በላይ የጋራ ዕሴትን በማጠናከር በአንድነት ሠርቶ ወደ ህዳሴው ለተጀመረው ጉዞ ሕገ መንግሥቱ የጣለውን ፅኑ መሰረት በመገንዘብ ነው። ስለዚህም ለብዝሃነታችን ዕውቅና በመስጠት ለህዳሴው ጉዞ መሰረት የጣለውን ሕገ መንግሥት እናክብረው፣ እናስከብረው።

 

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።