Items filtered by date: Monday, 04 December 2017

     

                                                                                                           አቶ አድማሱ ሳጂ               ማስተር ኪሮስ ገብረመስቀል

 

«የማርሻል አርት፣ የካራቴ፣ የቴኳንዶ...» ስልጠናን የሚጠቁሙ ማስታወቂያዎችን በከተማዋ የተለያዩ ስፍራዎች ላይ ማስተዋል የተለመደ ነው። በኤሌክትሪክ ፖሎች ላይ ሳይቀር ተለጥፈው እንዲመዘገቡ የሚጋብዙት ማስታወቂያዎች እንደ አሸን ፈልተዋል። በማስታወቂያዎቹ መሠረትም በርካታ ህጻናት፣ ወጣቶች እና ጎልማሶች የማዘውተሪያ ስፍራዎቻቸው እያደረጓቸው ነው። ይሁንና እነዚህ አካላት መሰል ስልጠናዎችን ለመስጠት ምን ያክል የክህሎት እና ሳይንሳዊ ብቃት አላቸው? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ነበረበት። ይሁን እንጂ ሁሉም የብቃት ማረጋገጫ ሳይኖራቸው እንደሚሰሩ ይታወቃል።

እነዚህ ባለሙያዎች ለዚህ የሚያበቃ የሙያ ብቃት፣ ባለቤትነት እና ዝግጁነት? በሰልጣኞቹ ላይ ሊደርስ በሚችለው አካላዊ እና አዕምሯዊ ጉዳት ተጠያቂነታቸው እስከምን ድረስ ነው? ከመንግሥት አካላት ጋር ያላቸው ትስስርስ ምን ይመስላል? በሚሉትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚመለከታቸው አካላት ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

የቴኳንዶ ስፖርት ባለሙያው ማስተር ኪሮስ ገብረመስቀል፤ አንድ ስፖርታዊ ስልጠና ለመስጠት የተዘጋጀ ባለሙያ ለሌላ አካል አገልግሎት ከመስጠቱ በፊት ራሱን በሳይንስ እና በአካል ጥንካሬ መብቃት ይጠበቅበታል ይላሉ። ከሚመለከታቸውና ዘርፉን ከሚመራው አካል ህጋዊ እውቅና ማግኘትም ግዴታ ነው። ለባለሙያው እውቅና የሚሰጠው አካልም የስፖርቱን ከባድነት በመገንዝብ መመዘኛውን ከሰዎች ደህንነት አኳያ ማጤን አለበት። ይሁንና በአገራችን በአሁኑ ወቅት ባለው ነባራዊ ሁኔታ ህጋዊ ፈቃድ ካለው ይልቅ የሌለው ይበዛል። የሚል እምነት አላቸው።

ፈቃድ አሰጣጡም ጠንካራ እና የተጠያቂነት ማዕቀፉን ያዘለ አይደለም፡፡ በዚህ አጋጣሚም በርካታ ሰዎች ለአካላዊ እና አዕምሯዊ ጉዳት እየተዳረጉ መሆኑን መገመት አያዳግትም ባይ ናቸው፡፡ በሌላው ዓለም ተጎጂው ለሚደርስበት ቀላልም ሆነ ከባድ ችግር ማዕከሉ በቀዳሚነት ተጠያቂ የሚሆንበት አሰራር አለ፡፡

እነዚህ የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላት ሲበራከቱ አያሌ ጥቅሞችን ይዘው እንደሚመጡ ሁሉ የሚያስከትሏቸው ችግሮችም በዚያው ልክ በመሆኑም ከወዲሁ መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ነው የሚጠቁሙት፡፡ የሙያው ጥራት ማስጠበቅና ህጎች ሲወጡ ያላቸውን እውቀት ማካፈል ብሎም ተተኪዎችን በማፍራት እና በማብቃት ረገድ ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡

በዚህ ረገድም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ ውስን ነው፡፡ አንዳንድ ባለሙያዎች ይህን ኃላፊነት የሚወጡ ቢሆኑም፤ በስፋት አሳታፊ ለመሆን የስፖርት ቢሮዎችና የሚመለከታቸው አካላት በሮች ለባለሙያዎች የተከረቸሙ መሆናቸውን ነው የሚያብራሩት፡፡ በዚህም የተነሳ ውጤታማነት ርቋቸዋል የሚል አቋም አላቸው፡፡

እንደ ማስተር ኪሮስ አስተያየት፤ በዚህ ረገድ መንግሥት ቀዳሚውን ሚና ከሚጫወቱ አካላት አንዱ ነው፡፡ የመንግሥት ኃላፊነት ስፖርት የሚያዘወትሩ ዜጎችን አቅም በፈቀደ መጠን መደገፍ ይጠበቅበታል፡፡ በሌላው ዓለም ያለውን ተሞክሮ በመቀመር እና ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ስፖርቱ ዘመናዊና ሳይንሳዊ ጥበብ የሚሆንበት ፖሊሲ መዘርጋት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ለይደር የማይተው ጉዳይ ነው። የሚል ሙያዊ አስተያየት ይሰጣሉ፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ የመንግሥት ሚና መልካም እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ አቅም በፈቀደ መጠን የፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ የአሠራር ሥርዓቱ እንዲስተካከልና እንዲዘምንም ተከታታይ መመሪያዎችን ወደ ታችኛው እርከን ያወርዳል፡፡ ይሁንና አንዳንዴ የሚስተዋሉ የአስፈጻሚ አካላት የአቅም ውስንነት ብሎም አዳዲስ አሠራሮችን አለመሻት ስፖርቱን አሽመድምዶታል፡፡

ለሁሉም ስፖርቶች ወጥነት የጎደለው ዕይታ መጓደል እና ሳይንሳዊ አሰራር አለማስረፅም ሌላኛው ፈታኝ ጉዳይ ነው፡፡ ለውጥ ለመፍጠር ፍላጎት ቢኖርም የተነሳሽነት ስሜት ይጎድላል፡፡ ባለሙያዎችን ማቅረብና በጉዳዮች ላይ በጋራ መወያየት እንዲሁም መመካካር ላይም ክፍተት ይስተዋላል፡፡ በአነስተኛ ውድድር እና ጥቅም አልባ ወጪ ላይ በማተኮርም ጊዜና ጉልበት ይባክናሉ፡፡ ይህም የስፖርት አካሄድ ከሌላው ዓለም ጋር ሲነፃፀር ቀርፋፋ አድርጎታል የሚል ምልከታ አላቸው፤ ማስተር ኪሮስ፡፡

አቶ አድማሱ ሳጂ በኮተቤ ሜትሮፖሊቲያን ዩኒቨርሲቲ የስፖርት መምህር ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ጂምናስቲክ ፌዴሬሽ በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለ 11 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ አባል ሆነውም ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከ2001 እስከ 2009 .ም መጨረሻ ድረስ ደግሞ የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ነበሩ፡፡ በዚህም የተነሳ ከእነዚህ ስፖርቶች ጋር የቅርብ ትውውቅ አላቸው፡፡ በየአካባቢው የሚከፈቱ የስፖርት ማዕከላት በሁለት መልኩ መቃኘት መልካም እንደሆነም ይጠቁማሉ፡፡ በግል ተቋማትም ሆኑ በማኅበረሰቡ የጋራ ጥረት የሚመሰረቱ የስፖርት ቤቶች ለተቋቋሙለት ዓላማ ለአካባቢው ፈርጀ ብዙ ጠቃሜታ ያበረክታሉ፡፡ ትልቅ የገቢ ምንጭና የአቅም መገንቢያም ናቸው፡፡ ማኅበረሰቡ የሚዝናናበት እና ማህበራዊ ግንኙነት ለማጠናከር ብሎም ጤናማ ማኅበረሰብን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ሚናው የጎላ ነው፡፡

ለአብነት ካራቴ፣ ቴኳንዶ ወይም ውሹ ተብለው የሚከፈቱ ማዕከላት በስፖርት የስልጠና መርህ እና በአግባቡ ከተሰጡ እና በብቁ ባለሙያ ከታገዙ ከህፃናት እስከ አዋቂ የስፖርት ክህሎት በመስጠት እና የተወዳዳሪነት መንፈስ በመፍጠር ብሎም አካላዊ ብርታት እና ጥንካሬ በመፍጠር ረገድ ፋይዳቸው ተስተካካይ የለውም፡፡ በተለይ ህጻናት በመሰል ስፖርት ሲሳተፉ ሥነ ምግባር ለመላበስ፣ በጋራ የሚሰሩ ሥራዎችን ለማቀላጠፍ እንዲሁም ስሜታቸውንና ፍላጎታቸውን ለመቆጣጠር ያግዛቸዋል፡፡ አዋቂዎችም ለጤናቸው በረከት፤ ማኅበራዊ መስተጋብራቸውም እንደ አለት የጠነከረ ይሆን ዘንድ ይጠቅማል፡፡

አቶ አድማሱ እንደሚሉት፤ እነዚህ ማዕከላት የሚሰጡት ስልጠና እንደ አካል ብቃት ሲታይ ደግሞ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የስፖርት ግብዓት ማሟላት አለባቸው፡፡ የሚሰጡት የአካል ብቃት ስልጠናም ከጠቀሜታው እና ከዓላማው አኳያ ሊቃኝ ይገባል፡፡ ስልጠናው ምን ያክል አቅም ገንቢ ነው፣ በምን ደረጃ ይሰጣል የሚለውም ታሳቢ መደረግ አለበት፡፡ በስፖርቱ አስፈላጊውን ጥበብ እና ክህሎት ለማሳየትም አካል ብቃት መሰረታዊ ጉዳይ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡ በዚህ ረገድ በአገሪቱ የሚስተዋለው ችግር የስፖርቱ አሰልጣኝ የአካል ብቃት እና ጥበብ በተናበበ መንገድ ያለመከናወኑን ነው፡፡ ስፖርት ደግሞ በዚህ መንገድ ካልተዘወረ አደጋን ይጋብዛል፡፡

«መሰል ስፖርቶች ሲከናወኑ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ አካላዊ መዋቅር በጠበቀ መልኩ መሰጠት ይኖርባቸዋል፡፡ በሰውነት ውስጥ ያለውን የስብ ክምችት፣ የአተነፋፈስ ስርዓት፣ የደም ዝውውር እና የውስጣዊ ኃይል አጠቃቀምን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆንም አለበት፡፡ መሰረታዊ ሰውነት መዋቅርን የሚጎዳ ስፖርት መሰጠት የለበትም፡፡ በተለይ የሰውነት መገጣጠሚያዎች ተፈጥሯዊ መዋቅራቸው እንዳይናጋ መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ለዚህም ሳይንሳዊ መርሆችን በጥንቃቄ መገንዘብ ይሻል፡፡ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ወቅትም ባለሙያው ሰልጣኞች አደጋ እንዳይደርስባቸው በሳይንስ የተደገፈ እና በትክክለኛ መንገድ እንዲከናወን ሙያዊ ግዴታ ነው፡፡ በዚህ መልኩ የማይከናወን ከሆነ ግን አደጋው የከፋ ይሆናል» ይላሉ።

እንደ አቶ አድማሱ ማብራሪያ ከሆነ፤ በየሰፈሩ የሚከፈቱ ስፖርት ቤቶች በጥናት እና ዳሰሳ ባይደገፍም ባለሙያ ቀጥረው የሚሰሩ እና ግብዓት የሚያሟሉት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ይሁንና አብዛኞቹ የሚያገኙትን ገቢ ማዕከል በማድረግ የስፖርት ቤቶችን እንደሚጀመሩ ነው የሚጠቁሙት፡፡ ስለሆነም መሰል ተቋማት አስፈላጊውን ነገር ሳያሟሉ ወደእዚህ ሙያ መግባት የለባቸውም የሚል ምክር ይሰጣሉ፡፡ በእውቀት ደረጃ መርሁን ማወቅ ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ ይልቁንም ክህሎት በዚያው ልክ ማደግ አለበት፡፡ ይህ እንዲሆንም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል፡፡ ችግር የሚፈጥሩ ከሆነም የማስተካከያ እርምጃ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የጤና ጠንቅ የሚሆኑበት አጋጣሚም በአያሌው የበረከተ ነው፡፡ እውቀት እና ክህሎትም እንዲጣጣ እንደሌሎች ትምህርቶች የመስክ እና የልምድ ለውውጥ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በአገሪቱ በብዛት የተለመደው የስፖርቱን መርህ ብቻ እንዲይዙ እንጂ በተግባር ማስደገፉ ብዙም አይደለም፡፡ ተጠያቂነትን መሰረት ያደረገ ሥራ በብዛት እንደማይሰራ የሚናገሩት መምህር አድማሱ፤ በዚህ ላይ በአግባቡ ፈትሾ እውቅና የሚሰጥበት አሰራር መዘረጋት ተገቢ መሆኑን ይገለፃሉ፡፡ የተጠያቂነት ሥርዓትም ተግባራዊ መሆን አለበት፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም መጠነኛ ስልጠና ወስደው የሚገቡ አካላት ሊደነቁ እንደሚገባ ይናገራሉ።

«በአሁኑ ወቅት በየፈሰሩ የሚገኙ የስፖርት ማዕከላት መስመር እንዲይዙ እና በህግ እንዲዳኙ መሠረታዊ ሥራዎች መከናወን አለባቸው፡፡ ይህንን በዋናነት ለመከታተልም በአገር አቀፍ ደረጃ ስፖርቱን የሚመራው አካል ቀዳሚ መሆን አለበት፡፡ ያሰለጠነውን እና እውቅና የሰጠውን አካል በተሰማራው የሥራ መስክ ህብረተሰቡን እየጠቀሙ ከሆነ ማጠናከር፣ ችግር ያለባቸውን ደግሞ እንዲታረሙ ማደረግ አለበት፡፡ ዘርፉን የሚመሩ አካላትን አሰልጥኖ ከመልቀቅ ባለፈ መቆጣጠር እና ትክክለኛውን መስመር ማስያዝ ላይም የተለመደ አይደለም፡፡ ይሁንና መሰል ስፖርቶች ወቅታዊ ግኝቶችን ተለዋዋጭ የሆነ ሳይንስ በመሆኑ፤ በየጊዜው ሊፈተሽ ይገባል፡፡ ችግሮችም ሲደርሱ ተጠያቂ መሆን ያለበት ስልጠናውን እንዲሰጥ እውቅና የሰጠውና ስፖርቱን የሚመራው ተቋም እንዲሁም ንግድ ፈቃድ የሰጠው አካላት መሆን አለባቸው፡፡ በመሆኑም ስልጠናውን የሚሰጡ ባለሙዎቹ ከተጠያቂነት ሊያመልጡ አይችሉም» የሚል አቋም አላቸው፡፡

በውጭው ዓለምም ይህን እውቅና የሚሰጥ እና የሚከታታል አካል በቦርድ ይመራል፡፡ ይህም ከጤና፣ ከስፖርት፣ ከንግድ፣ ከወጣቶች እና ማህራዊ ዘርፍ ሚኒስትሮች የተውጣጣ ነው፡፡ ቦርዱም በሙያ ዘርፍ ተደራጅቶ ሊሰጥ የሚገባውን የስልጠና ዓይነት ይመክራል፡፡ በጋራ የሚሰራውን በማመላከትና ለችግሮችም መፍትሄ የሚያስቀምጥ ነው፡፡ ለዘርፉ ጠቃሚ የሆኑ ጥናትና ምርምሮችንም ያደርጋል፡፡ ኢትዮጵያም በዚህ መስመር ውስጥ ለማለፍ አስቸጋሪ እንደማይሆንባት ነው አቶ አድማሱ የሚያብራሩት፡፡

«እነዚህ ስፖርቶች በአግባቡ ካልተሰሩና በባለሙያ ካልታገዙ ከባድ የሆነ አካላዊ እና ሥነልቦናዊ ጫና ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ ተፈጥሯአዊ ተክለ ቁመናንም ያበላሻሉ፡፡ ውስጣዊ እይታን ከማበላሸት ባሻገር ውስጣዊ አተነፋፈስ እና የደም ዝውውር ላይም ችግር ይፈጥራሉ፡፡ የማርሻል አርት ስፖርቶች የሰውነት ማገጣጠሚያን በሰፊው ስለሚጠቀሙ መገጣጠሚያዎች ቦታቸውን የሚለቁ በመሆናቸው ሕይወት ላይ አደጋ እና ማሕበራዊ ቀውስም ያስከትላ» በመሆኑም በዘርፉ አስገዳጅ ህግ ሊኖር ይገባል የሚል አቋም አላቸው፡፡

«በስፖርታዊ እቅስቃሴ ወቅት ለሚደርሱ ችግሮች የማዕከላቱ ባለቤቶችና የሚመለከታቸው አካላት ተጎጂዎችን ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነዚህ ተቋማት ጥቅም ሲያገኙ እንዲሚደሰቱ ሁሉ፤ ለሚደረውሰው ጉዳትም መጠየቅ አለባቸው፡፡ ከዚህ በዘለለ ወደ ስፖርቱ ለሚገቡትም የጤና ምርምራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሚመጥናቸውን ስፖርት መስራትም አለባቸው፡፡ ስልጠናውን የሚሰጡ ተቋማትም ሆኑ ግለሰሰቦች ህጋዊ እውቅና እንዳላቸው የማረጋገጥ ኃላፊነትም አለባቸው» ይላሉ፡፡

ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከስፖርት ማህበራት ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው «ውሹ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፤ ኢንተርንናል ቴኳንዶ» እና መሳሰሉት በአጠቃላይ «ወርልድ ቴኳንዶ» የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ናቸው፡፡ የእነዚህ የፈቃድ አሰጣጥም የተለያየ ነው፡፡ እነዚህ ክለቦች ወይንም ማህበራት የብቃት ማረጋገጫ የሚሰጣቸው፤ የክለቦች ማቋቋሚያ እና መተዳደሪያ ደንብ ሲኖራቸው፣ ስልጠናውን ለመስጠት የሚያበቃ ብቃትና ደረጃ ሲያሟሉ፣ ማሰልጠኛ ወይንም የስፖርት ማዘውተሪያዎቹ ምቹ ሆነው ሲገኙ እና በቀድሞ 12ተኛ በአዲሱ ትምህርት ሥርዓት ደግሞ 10ኛ ክፍል ያጠናቀቁ ሲሆኑ ነው፡፡

ፈቃድ አሰጣጡም ከአዲስ አበባ ከተማ እስከ ክፍለከተማ ድረስ የተዋቀረ ነው፡፡ ለአብነት ያህል በወርልድ ቴኳንዶ እና ኢንተርናሽል ቴኳንዶ ሁለተኛ ዳን እና ከዚያ በላይ ከሆነ ፈቃዱ በከተማ ደረጃ ይሰጣል፡፡ ከሁለተኛ ዳን በታች ካለ በክፍለከተማ ደረጃ ይሰጣል፡፡ ለውሹና ካራቴ ስፖርቶች ጥቁር ቀበቶና ከዚያ በላይ ከሆነ በከተማ ደረጃ ይሰጣል፡፡ ከዚህ በታች ለሆኑ ቀበቶች ደግሞ በክፍለከተማ ደረጃ ይሰጣል፡፡ ይሁንና ባለሙያዎቹ ከተፈቀደላቸው ውጭ ስልጠና የሚሰጡ ከሆነና ጉዳት ከደረሰ ተጠያቂነት ይኖራል፡፡ ካልተሰጠው የስልጠና ዘርፍ እና ከብቃቱና ክህሎቱ ውጭም ሊያሰለጥን መተዳደሪያ ደንቡ ይከለክላል፡፡ እነዚህ የስፖርት ዘርፎች ወጣቶች አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ የሚታደጉ በመሆናቸው፣ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል የፈጠሩ በመሆናቸውና ትርፍን ማዕከል ያደረጉ ባለመሆናቸው ለስፖርት ማህበራትና ክለቦች ስለሆኑ ይበረታታሉ፡፡

እንደ ዳይሬክቶሬቱ መረጃ፤ የብቃት ማረጋገጫ አኳያ በአሁኑ ወቅት ብዙም እየሰራበት እንዳልሆነ ነው የተገለጸው፡፡ አሰራሩ ወደ ተቋሙ ሲመጣ የሚተገበር ይኖራል፡፡ በአሁኑ ወቅት «ዳኞች» እና ጥቁር ቀበቶ ያላቸው ግለሰቦች በብሄራዊው ፌዴሬሽን ተመዝነው ነው ተቀባይነት የሚያገኙት፡፡ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና የሚወስዱት በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና በዲፕሎማ ወይንም በተቀመጠው ደረጃ የተማሩት ናቸው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን እነዚህ 10ኛ እና 12ተኛ ክፍል ያጠናቀቁ ነገር ግን በዚህ ሥርዓት ውስጥ ያልገቡ ናቸው፡፡ በከተማዋ የሚስተዋሉ የስፖርት ቤቶች በብቃት ማረጋገጫ እንዳላለፉ ነው የተገለፀው፡፡ የብቃት ማረጋገጫውም እንደ መስፈርት አልተቀመጠም፡፡

አቶ አበራ አመንቴ የአዲስ አበባ የምዝና አገልግሎት ዝግጅትና አሰጣጥ ዳይሬክተር ናቸው። እነዚህ የስፖርት ማዕከላትን ከፍተው ደንበኞችን የሚያሰለጥኑ አካላት መበራከታቸውን ያምናሉ፡፡ ይሁንና ተቋማት ከማሰልጠን ባለፈ ሲያስመዝኑ አንመለከትም ብለዋል፡፡ በዚህ ውስጥ ያለፈ ተመዛኝም ማግኘት አይቻልም ነው የሚሉት፡፡ «መዛኝ፣ የምዘና ጣቢያ እና የምዘና ግብዓቶች ቢሟሉም ምዘናው ግን የውሃ ሽታ ሆኗል። ሰልጣኞችን ማሰልጠን እንጂ ተመዛኙ ሲመዘን አናይም» ይላሉ፡፡ ይሁንና በዚህ ሂደት ውስጥ ሳያልፍ የአሰልጣኝነት ፈቃድ መስጠቱን ይኮንናሉ፡፡ ይህንንም የሚከታታለው እና ፈቃድ የሚሰጠው የአዲስ አበባ ወጣችና ስፖርት ቢሮ ነው፡፡ ታዲያ ሳይመዘኑ ስለምን ፈቃድ ይሰጣል? ሲሉ ጥያቄውን በጥያቄ ይመልሳሉ፡፡

እንደ ህጉ ከሆነ፤ ያልተመዘነ ሰው አሰልጣኝ መሆን የለበትም፡፡ ከዚህም ባሻገር ህጉ አስገዳጅ ነው፡፡ በጤና፣ በግንባታ፣ የመሳሰሉት ላይ ያሉ መዛኞችም ሆኑ ተመዛኞች በአሰራሩ መሠረት እየሰሩ ሲሆን በዚህ ዘርፍ ያለው ግን አስቸጋሪ እንደሆነ ነው የሚጠቁሙት፡፡ «እነዚህ አካላት ወደ ብቃት ማረጋገጫ ማዕከል መምጣት አለባቸው፡፡ እንዲመጡም የቴክኒክና ሙያ ስትራቴጂ ያስገድዳል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም መቀጠል የለበትም፡፡ ሳይመዘኑም በፍጹም መስራት የለባቸውም» ይላሉ፡፡

ጉዳቶችም ሲደርሱም ከተጠያቂነት የሚያመልጡ አይሆኑም፡፡ እነዚህ ሥራዎችም ገንዘብን ማዕከል ያደረገ እንቅስቃሴ ላይ የሚያተኩሩ መሆን የለባቸውም፡፡ ስለሆነም ህግና ደንብን ተከትለው እንዲንቀሳቀሱ እና ብቃትን ማዕከል ያደረገ አሰራር መከተል እንደሚገባም ነው አቶ አበራ የሚያሳስቡት፡፡

 

ክፍለዮሐንስ አንበርበር

 

Published in ስፖርት

አዱሊጣ የሚለው ቃል ኦሮምኛ ሲሆን ትርጓሜውም ፀሐይ ግባት (sun set) ማለት ነው። አዱሊጣ የኮንፈረንስ፣ የፍልውሃ፣ የመዝናኛና የእንግዶች ማረፊያ ሆቴል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በቢሾፍቱ ከተማ ለሚያስገነባው ራዲሰን ብሉ ቢሾፍቱ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ልማት፤ አስተዳደር ካርልሰን ሬዚዶር ሆቴል ግሩፕ ከተባለውና መቀመጫውን ብራስልስ (ቤልጅም) ካደረገው ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራረመ። ራዲሰን ብሉ ቢሾፍቱ ከአዲስ አበባ 35ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘ ቢሾፍቱ ከተማ በ800 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚገነባ ሲሆን፣ ከ2ሺ በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው ተብሏል። የሆቴሉ ግንባታ ከ3 እስከ 4ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ እና ወደ ሥራ እንደሚገባ ታውቋል።

ራዲሰን ብሉ ቢሾፍቱ ሥራ ሲጀምር ለመደበኛ፣ ለከፍተኛና ለፕሬዚዳንታዊ ደረጃ የሚሆኑ 152 የመኝታ ክፍሎች ይኖሩታል። 1045 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ያረፈ የላቀ የጥበብ ደረጃ የያዘና እስከ 1500 ሰዎች ማስተናገድ የሚችል ዘመናዊ የሰርግ እና የመዝናኛ አዳራሽ ይኖረዋል። 6 ዘመኑን የሚመጥኑ ከ20 እስከ150 ሰዎችን መያዝ የሚችሉ አነስተኛና መካከለኛ የኮንፈረንስ ክፍሎች ይኖሩታል። 800 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የአካል ብቃት ማእከል እንዲሁም የራሱ መዋኛ ገንዳ ያለው ጂም ተካተውበታል። 5 የሙሉ ቀን መመገቢያዎች ልዩ ሬስቶራንቶች (ስፔሻሊቲ)፤ የአገር በቀል መናፈሻ ዛፎች፤ ቦታኒካል ላውንጅ፤ ባለሰገነት መዝናኛዎች፣ የባቡጋያ ሀይቅ የፀሐይ መግቢያን የሚያሳይ ሰገነት ይኖሩታል።

በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን ከማስገኘቱም በላይ ለቢሾፍቱ ከተማ እና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኝ እንደሚሆን ተነግሮለታል። የአገሪቱን መደበኛ ጎብኚዎች ብሎም የኮንፍረንስ ቱሪዝምን ለማሳደግ የራሱን አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው ተብሏል።

ራዲሰን በሉ ቢሾፍቱ ሆቴል ግንባታን ለማስጀመር በአዱሊጣ ሆቴል ኩባንያና ካልርሰን ሬዚዶር ጋር ህዳር 21ቀን 2010 .ም በአዲስ አበባ በሚገኘው ካሳንችስ በራዲሰን ብሉ ሆቴል ውስጥ የፊርማ ሥነሥርዓት ተካሂዷል።

የራዲሰን ብሉ ቢሾፍቱ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ግንባታና የሆቴል ሥርዓቶችን እንዲያስተዳድር የተፈራረመው ሬዚዶር ሄቴል ግሩፕ ከዓለም ቀዳሚ ከሆኑ የሆቴል ግሩፕ መደቦች አንዱ ሲሆን ዓለም ላይ ከ80 በላይ በሆኑ ሀገራት በድምሩ 106ሺ ክፍሎች ያሏቸው 480 ታላላቅ ሆቴሎችን የሚያስተዳድር ነው። በአውሮፓ፣በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ ውስጥ ለ44ሺህ ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ኩባንያ መሆኑም ይታወቃል። የራዲሰን ብሉ ቢሾፍቱ ባለአምስት ኮኮብ ሆቴል ባለቤት የላይንሰ ትሬዲንግ (ላየንስ ግሩፕ) ባለቤት የሆኑት አቶ ጌታቸው ወርቁና ቤተሰቦቻቸው መሆናቸው በፊርማ ሥነሥርዓቱ ላይ ተጠቁሟል። ግንባታው በመጪው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

 

ግርማ ለማ

 

 

Published in መዝናኛ

 

ልብ ወለድ

ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ ይጀምራል። ልጆቼ በየተራ ይመጣሉ፤ የትምህርት ቤት ክፍያ፣ የትራንስፖርት፣ በትምህርት ቤት ለሚሠራ የቡድን ሥራ...ምክንያታቸው ይለያይ እንጂ ጥያቄያቸው ግን ያው ገንዘብ ነው። የሚገርመኝ አጠያየቃቸው ነው፤ ኮስተር ያለ ትዕዛዝ አዘል ቃና አለው። ጥቂት ሳይቆይ «እህ ጌታው ቀለብ ማለቁን አልነገርኩህምትለኛለች ባለቤቴ በተራዋ፣ ገንዘቡን ስሰጣት ንግግሯን እንኳን አላስጨርሳትም።

«ማታ ስትመጣ አንዳንድ ነገር ይዘህ መምጣት እንዳትረሳ» ትለኛለች እግሬን ከማንሳቴ። ሌላ ትዕዛዝ ሳይከተልብኝ ከቤቴ ለመራቅ እፈጥናለሁ። በር ላይ ከመድረሴ ትንሿ ልጄ እየተጣራች ስትከተለኝ አያታለሁ። «እርሳሴ አለቀብኝ» ትለኛለች አሻቅባ ዓይን ዓይኔን እየተመለከተች። የእርሷ አጠያየቅ ከሌሎቹ ይሻለኛል። ቢያንስ ለሰጠኋት የእርሳስ መግዣ በመሳም ምስጋናዋን ታደርሳለች።

ታክሲ ተራ ስደርስ ተዋክበው የሚያዋክቡ የታክሲ ረዳቶች ጩኸት፣ «እኔ ጋር ግባ፣ በዚህ ታክሲ ሂድ...» የሚሉ ጉትቻዎች፣ በታክሲ ግፊያ የሚኖሩ መጎሻሸሞች፣ መረጋገጦችና መረጋገሞች ሁሉ በህግ የተፈቀዱ እስኪመስል ይቅርታ የማያስጠይቁ ጉዳዮች ሆነዋል።

ይህን ሁሉ አልፌ፤ ታክሲ ውስጥ ገብቼ ከመቀመጤ «የት ነውይለኛል ሌላኛው ኮስታራ መንገደኛ። አጠያየቁ የሰራሁት ስህተት አሊያም ያጠፋሁት ነገር ያለ እስኪመስለኝ የቁጣ ነው። አቅጣጫውን ከመናገሬ፤ ረዳቱ በጉርምስና ያበጠ ደረቱን ነፍቶ «ተጠጋ» ይለኛል። ትዕዛዝ ነውና ወንበሩ ሁለት ሰው የመያዝ አቅም እንዳለው እያጉረመረምኩ ለሦስተኛው ሰው እጠጋለሁ።

አንዳንዴ ለረዳቱ ከምሰጠው ብር ላይ መልስ ይኖረኝና እጠይቃለሁ፤ «ዝርዝር የለኝማየሚል ማስጠንቀቂያ አዘል ምላሽ ይደርሰኛል። ድጋሚ ብጠይቅ ስድብና ያልሆኑ ቃለ ምልልሶች ስለሚከተሉኝ ዝምታን እመርጣለሁ።

ለእነርሱ ትህትና ማጣት ግብረ-መልሴ ቁጣ ቢሆን ጉዳቱ ወርዶ ወርዶ በየሦስት ቀኑ እርሳስ እስከሚያልቅባት ትንሿ ልጄ ይደርሳል። ምክንያቱም አልጠጋም ብል «ውረድ» መባሌ አይቀርም፣ ሌላ ታክሲ ጥበቃስ ሰዓቴ መቃጠሉ አይደል? ያው ፊርማው ከተነሳ ደግሞ የደመወዝ ቅጣት አይቀርልኝ፣ ደመወዜ ተቆረጠ ማለት ደግሞ፣... ይታያችሁ እንግዲህ ይህ ሁሉ በእኔ ህይወት ላይ የሰለጠነ ነው።

በመንገዴ ይህንን ውጣ ውረድ አሳልፌ መሥሪያ ቤቴ ደጃፍ ስደርስ ለፍተሻ የተዘጋጁ ጥበቃዎች፤ የጦር መሳሪያ የታጠኩና ያልተፈቀደ ነገር ይዤ የተገኘሁ እስኪመስለኝ ቆፍጠን ብለው ቦርሳዬን መበርበር ይጀምራሉ። አካላቴን ሲፈትሹማ በደም ስሬ የደበቅኩት አንዳች ነገር ያለ እስኪመስል ጠበቅ አድርገው ነው። ሥራቸውን አከብራለሁ፤ ነገር ግን «እንዴት አደሩ፣ ለፍተሻ ይተባበሩን...» ብሎ መፈተሽ ሲቻል ከፍተኛ ጉልበትና ኃይል ማባከናቸው ይገርመኛል። ብቻ የቦታው አለቃ እነርሱ ናቸውና እታዘዛለሁ።

የቀን ውሎዬም ያው ነው። የአለቃ ግልምጫ፣ የባልደረባ ንትርክ፣ የባለጉዳይ እሮሮ...ብቻ ሁሉም ጋር ቁጣ፣ ትእዛዝና ማስጠንቀቂያ ነግሰው ይታዩኛል። እቃ ለመግዛት ጎራ ባልኩባቸው ቦታዎች የዋጋ መናር ሳነሳ «ካልገዛህ ተወው» የሚል ምላሽ ማግኘቴ ያስገርመኛል። የሚገርመኝ ቁጣቸው ብቻ ሳይሆን፤ ስራቸውን የሚሰሩበት መንገድም ነው።

በጎዳናው በሚፈሰው ህዝበ አዳም ዘንድ ትንንሽ ስረወ-መንግስቶች መመስረታቸው ይታየኛል። አብዛኛው ሰው በራሱ ላይ የራሱን ዘውድ ጭኖ የነገሰ ፈላጭ ቆራጭ ነው። ታዲያ እነዚህ ተቀናቃኝ ትንንሽ መንግስታት በየት በኩል ሊስማሙ ይችላሉ? ትንሿ ልጄና እኩዮቿ ላይ የምመለከተው አጠያየቅና የምስጋና አቀራረብ ሲያድግ አላየሁም። ህጻናቱ የሚያድጉት በትህትና ላይ ተረማምደው እስኪመስለኝ መልካምነት ሞታ ትእቢት ትፈነጫለች።

እኔ «ከነገሩ ጾም ይደሩ» ብዬ ራሴን ባሳንስም የአንዳንዱ ድርጊት ግን እኔን ተጠቂ ማድረጉ አልቀረም። በረግረጋማ ቦታ ላይ እንደተገኘ ደረቅ መሬት ሁሉም ተረማምደውኝ ሲያልፉ መመልከት፤ ቁጣና ዛቻም ትክክለኛ ሆነው መገኘታቸው ግራ ቢገባኝም ለመቀበል እጥራለሁ። ማረቅ ባልችልም በልጆቼ የሚሰጡኝን ግዳጆች፣ የሚስቴን ቀጭን ትእዛዝ፣ የታክሲ ተራውን ማስፈራሪያ፣ የጥበቃዎቹን ዱላ ቀረሽ ፍተሻ፣ የአለቃን ግልምጫ፣ የባልደረቦቼን ንትርክና የባለጉዳይን እሮሮ ሁሉ ተለማምጄዋለሁ።

ከሥራ ሰዓት ውጪ እግሬ የጣለኝ ቦታ ላይ ተገኝቼ የሰውን ስሜት ለማጤን እሞክራለሁ። ሁሉም ችኩል፣ ሁሉም ለራሴ ብቻ ባይ፣ ሁሉም ኮስታራ፣ ሁሉም ተቆጪ ... ከማያቸው በርካታ ፊቶች የማገኘው ጥቂት ትህትና ብቻ ነው። ይህም «ትህትና ወደ የት ተሰደደችእንድል ያስገድደኛል። መልስ ለማግኘት ጥያቄን በትህትና ማቅረብ፣ «መብቴ ነው፤ ግዴታህ ነው» ከማለት በፊት ትብብር መጠየቅ፣ «ብትፈልግ አድርግ፤ ባትፈልግ ተወው» ከሚል አማራጭ ጉዳዩን ማስረዳት ቢቀድምስ? እያልኩ አስባለሁ።

እንዲህ እያለም ቀኑ ይመሻል። የሰውን ስነምግባር እንዲሁም ቦታ አጥታ ስደት ስለወጣችው ትህትና እያሰብኩ ጠዋት የታዘዝኩትን ረስቼ ቤቴ እደርሳለሁ። ለምን እንደረሳሁት የማስረዳበት ዕድል አላገኝም፤ «እንዴትእንዳትሉኝ፣ ምክንያቱም የሚስቴ ቁጣ ...

 

ብርሃን ፈይሳ

 

Published in መዝናኛ

 

በጤና ተቋማት ባለሙያ ሆኖ የተቀጠረ ግለሰብ፤ ሊታከም ጎራ ያለን ሰው ህመሙን ምንነት ሳያረጋግጥ መድሃኒት ቢያዝ ምን ሊከሰት ይችላል? ውሳኔ የሚያስፈልገው ትልቅ ሃገራዊ ጉዳይ ብቃት በሌለው ሙያተኛ ቢሰየምስ? ስነ-ምግባር የሌለው መምህርስ መልካም ትውልድ ሊቀርጽ ይችላል? ሙያውን በቅጡ ያላወቀ ጉዳይ አስፈጻሚ ኃላፊነት ቢሰጠውስ ምን ሊከሰት ይችላል? የሚሉ ጥያቄዎች ቢነሱ መልሱ ከባድ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን የተጠቀሱት ዓይነት ግለሰቦች ቁጥር በርከት ያለ ቢሆን ሃገር ወደየት ሊያመራ ይችላል? ለሚለው ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ አስደንጋጭ መሆኑ አይቀርም።

ያለቦታቸው የተቀመጡት ግለሰቦች ብቃት ማነስ ምንጭ ሊሆን የሚችለው «ባለሙያ» የሚል ማረጋገጫ የሰጧቸው የትምህርት ተቋማት ናቸው። የትኛውም ግለሰብ ባለሙያ ሊባል የሚገባው በእውቀትና ክህሎት ብቁ ሆኖ ሲገኝ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ስራና ሙያን ከመበደልም አልፎ ሃገር ልታገኘው የሚገባትን ጥቅም ልታጣ ትችላለች። ማሰልጠን በሚገባቸው ልክ ያላሰለጠኑ የትምህርት ተቋማት ደግሞ ለዚህ ሀገራዊ ጥፋት ኃላፊነቱን መውሰዳቸው የግድ ይሆናል።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ክልሎች የተጀመረውና እየታየ የሚገኘው የሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች የማጣራት ጉዳይም ከዚህ ጋር ሊያያዝ የሚችል ነው። ብቃት በሌላቸው ተቋማት መሰልጠን በሃገር ዓቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን የብቃት መለኪያ ውጤታማ ሊያደርገው አይችልም።

መንግሥት በትምህርት ዘርፍ ከሚያከናውነው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ጎን ለጎን የግል የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ለዜጎች አማራጭ የትምህርት ማግኛ ከመሆናቸውም በዘለለ መንግሥት ካልደረሰባቸው ስፍራዎች ድረስ ዘልቀው የድርሻቸውን በማበርከት ላይ መሆናቸው ይታመናል። በዚህ ወቅት በሃገሪቷ ያሉት ከ120 በላይ የሚሆኑ የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለያዩ የትምህርት መስኮች ተማሪዎችን በማሰልጠን የተማረ ዜጋን በማፍራት ለሃገሪቷ ልማት ግብዓት የሚሆኑ ዜጎችን በማፍራት ላይ መሆናቸው አይካድም።

ይሁን እንጂ ከዚህ ዓላማ ውጪ በሆነ መንገድ ትውልድን በመልካም ስነምግባር የመቅረጽ ሳይሆን በተቃራኒው የተሰማሩ አልጠፉም። ሙያዊ ስነ-ምግባራቸውን ወደ ጎን በማድረግ በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የተሰጣቸውን መመሪያ ጥሰው የተገኙም ቀላል የሚባሉ አይደሉም። ባልተፈቀደላቸው መርሃግብር እና ካምፓስ ተማሪዎችን አሰልጥነው እስከማስመረቅ የደረሱ፤ የተቀመጠውን ስታንዳርድ አክብረው የማይሰሩ፤ ቋሚ መምህራንን የማይቀጥሩ፤ ከሚመለከተው አካል ሳይፈቀድላቸው ካምፓስ የሚቀይሩ፤ከተፈቀደው ክሬዲት ሃወር በላይ ወይም በታች የሚያስተምሩ፤ ከተፈቀደ የተማሪ ቁጥር በላይ የሚቀበሉ፤ ተገቢ ባልሆነ የትምህርት ማስረጃ ተማሪዎችን የሚያሰለጥኑና የተቋማት የመረጃ አላላክ፤ በህገወጥ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ተቋማት መኖራቸው ተረጋግጧል።

ከእነዚህ ተቋማት የሚወጡ ሰልጣኞች ከሌሎች ጋር ተወዳዳሪ መሆን እንደማይችሉ አያጠያይቅም። እውቅና ባልተሰጠው ፕሮግራም በመማራቸው ለገንዘብ፣ ለጊዜ እና ለእውቀት ብክነትም ይዳረጋሉ። ሙያዊና ስነ-ምግባራዊ መስፈርቶችን ባለማሟላታቸው ተገቢውን አገልግሎት አለመስጠት እና ሙያዊ ጥሰት ሊያደርሱም ይችላሉ። በተለይ በጤና ባለሙያዎች ብቁ አለመሆን በሚከሰተው የሰው ህይወትና አካል ጉዳት ተጠያቂ ከመሆን አይድኑም። ከዚህ ባሻገር የተቀመጠውን መመሪያ አክብረው በሚሰሩት ሌሎች የግል የትምህርት ተቋማት ላይ የሚኖረው እምነትም የሚሸረሽር ይሆናል።

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ በዲግሪና በድህረ ምረቃ ትምህርት ስልጠና የሚሰጡ የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፤ ትምህርትና ስልጠናውን ደረጃውን ጠብቀው እንዲሰጡ፤ ተማሪዎችም እውቅና እና የእውቅና ፈቃድ እድሳት በተሰጣቸው ተቋማትና የስልጠና መስኮች ብቻ እንዲማሩ፤ እንዲሁም በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛል። ለዚህ ይረዳ ዘንድ ኤጀንሲው ለተጠቃሚው ሕብረተሰብ የእውቅና ፈቃድ እና የእውቅና ፈቃድ እድሳት ያገኙትን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትንና ፈቃድ ያገኙባቸውን ካምፓሶች እና የስልጠና መስኮች ዝርዝር እንዲሁም በድንገተኛ ኦዲት የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ በየጊዜው ወቅታዊ መረጃ ይሰጣል። በሚያደርገው ድንገተኛ ጉብኝትም ደንቡን አክብረው በማይሰሩ ተቋማት ላይ እንደየጥፋታቸው መጠን ከማስጠንቀቂያ እስከ መዝጋት የሚደርስ እርምጃ ይወስዳል።

ይህ በተቋማት የመመሪያ ጥሰት የሚከሰት ችግርም ከግለሰቦች እስከ ሃገር ህልውና የሚደርስ ጉዳት ይኖረዋል። ይሁን እንጂ አሁንም በከፍተኛ ደረጃ በተቋማቱ የሚደርሰው ችግር ሊቀረፍ ባለመቻሉ ተቋማቱን በበላይነት ለሚቆጣጠረው ኤጀንሲ ራስ ምታት እንደሆነ ቀጥሏል። የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የ2009 .ም የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅትም፤ በ15 የትምህርት ተቋማት ላይ ባደረገው ድንገተኛ ጉብኝት የማስተካከያ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል። በተያዘው የበጀት ዓመትም 73 ድንገተኛ ጉብኝቶችን በማድረግ መመሪያና ደንብ በሚተላለፉት ላይ እንደየደረጃው የእርምት እርምጃ ለመውሰድ አቅዷል።

የችግሩ አስከፊነት አጠያያቂ ጉዳይ ባይሆንም ተቋማቱ መመሪያውን ተላልፈው ስለምን ያልተገቡ ተግባራት ላይ ይሰማራሉ የሚለውን መመልከት ያስፈልጋል። የችግሩን መነሻ ማወቅም መፍትሄውን ሊያመላክት ይችላል። በመሆኑም የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (በእነርሱ ተቋማት ችግሩ ባይንጸባረቅም) መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ በሚሉት ላይ ግን አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

የአፍሪካ የጤና ኮሌጅ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ መኮንን በላይ፤ ግልጽ የሆነ የአሰራር መመሪያ አለመኖሩ እንዲሁም የሚቀርቡ ጥያቄዎች ግብረ መልስ በፍጥነት ባለማግኘታቸው ችግሩ ሊከሰት አንደሚችል ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ያልተፈቀደን ነገር ማድረግ ተገቢ ባለመሆኑ ከተጠያቂነት ሊያመልጡ እንደማይገባም ያምናሉ። በመሆኑም ተቋማት «አገልግሎት አሰጣጡ ዘገየ» በሚልና በሌሎች ምክንያቶች ወደ ወንጀል መግባት የለባቸወም። የኤጀንሲው የሰው ኃይል በጣም አነስተኛ ነው፤ ስለሆነም ሊሰራ የሚችለው ባለው አነስተኛ አቅም ልክ ነው። ስለዚህም መንግሥት ኤጀንሲውን በሰው ኃይል በመደገፍ፤ በደንብ የተደራጀ እንዲሆን መታገዝ እንደሚገባው ይጠቁማሉ። ድርጅታዊ መዋቅሩም በዚያው ልክ መፈተሽ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፤ የኤጀንሲው መመዘኛ ትልቅ ቢሆንም የደመወዝ አከፋፈሉ ግን አነስተኛ በመሆኑ አሁን ባለው ሁኔታ ገበያው በሚፈልገው መጠን ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚቸገር ይናገራሉ። እንደሌሎች ሃገራት ተወዳዳሪ የጥራት ማዕከል እንዲሆንም አቅሙን ለማጎልበት ትኩረት መስጠት አንደሚገባ ያሳስባሉ ።

የጋምቢ የጤና እና ቢዝነስ ኮሌጅ ባለቤት ዶክተር ገበያው ጥሩነህ፤ የችግሩን ምንጮች በሁለት ይከፍሏቸዋል። የመጀመሪያው የስብዕና ችግር ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ «ሱሪ በአንገት አውልቁ የሚሉ መመሪያዎችና አፈጻጸሞች መሆናቸውን ይናገራሉ። በስብዕና ችግር ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ የሚሆነው ስብዕናው የተጠበቀ ትውልድ በመፍጠር ነው። ይህንን ለማከናወን ደግሞ የረጅም ጊዜ የሚሰራ በመሆኑ ጊዜያዊ መፍትሄዎችን መውሰድ አስፈላጊ ይሆናል። የመጀመሪያው ግልጽ የሆነ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ሲሆን፤ ይህንን ስርዓት ሊያስጠብቅ የሚችል «ጥርስ ያለው» ተቋም ማቋቋም ተከታዩ መሆን እንዳለበት ይጠቁማሉ። ሦስተኛው ደግሞ በኤጀንሲው የሚሰሩ እውቀትና ክህሎት ያላቸው እንዲሁም ስብዕናቸው በእውቀት የተገነባ ሰራተኞችን ማፍራት ነው። በማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ሥራ ስብዕናው የተጠበቀ ትውልድ እስኪፈጠርም ይህንን ማከናወን ተገቢ መሆኑን ነው ዶክተር ገበያው የሚያስረዱት።

የሃራምቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፈይሳ አራርሳ፤ ተቋማቱ ችግሩን የሚፈጥሩት ህግና ደንቡን ካለማወቅ፣ በትምህርት ስራ ውስጥ ልምድ ከማጣት እንዲሁም በግድየለሽነት ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ። ችግሮቹ፣ ተቋማቱ እንዲሁም ተቋማቱ ያሉበት ደረጃ በባህሪያቸው የማይመሳሰሉ በመሆኑ ምክንያታቸውም ይህ ነው ለማለት አስቸጋሪ እንደሚሆንም ይጠቁማሉ። አንዳንድ ችግሮች ደግሞ ከኤጀንሲው እና ከኤጀንሲው ሠራተኞች ሊመነጩ እንደሚችሉ ነው የሚጠቁሙት። ኤጀንሲው ካለው የአቅም ማነስ የተነሳም ለጥያቄዎች ፈጥኖ ምላሽ ካለመስጠት የሚከሰቱ ችግሮችም ይኖራሉ።

እነዚህ ችግሮች ሊቀረፉ የሚችሉትም የጋራ ኃላፊነትን እንዲሁም ተጠያቂነትን የሚያመላክቱ መመሪያዎች ሲኖሯቸው ይሆናል። ተቋማት የንግድ ፍቃድ አውጥተው፣ ሠራተኞችን ቀጥረው፣ የትምህርት ግብዓቶችን አሟልተውና አስፈላጊውን ነገሮች አጠናቀው እውቅና ሲጠይቁ ከአንድ ዓመት በላይ ሳይሰጣቸው ሊዘገይ ይችላል። በተቋሙ ላይ የሚደርሰው ኪሳራ ከፍተኛ ነው። በኤጀንሲው በኩል ለዚህ እንደ ምክንያት የሚነሳውም «በቂ ባለሙያዎች የሉኝም» የሚል መሆኑን ይገልጻሉ።

በኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ሞታ በበኩላቸው፤ ተቋማቱ እውቅና ለማግኘት ሲሉ አስፈላጊውን ግብዓት በተውሶ አሟልተው ለመታየት የሚጥሩ መሆኑን ይገልጻሉ። ይህም በድንገታዊ ጉብኝት የሚረጋገጥ በመሆኑ ተቋማቱ ቀድሞውንም አቅሙ እንዳልነበራቸው የሚያሳይ ነው የሚሆነው። ይህ ሁሉንም ተቋማት የሚመለከት ባይሆንም የተወሰኑ ተቋማትን የግድ ማሟላት እንዳለባቸው በማሳሰብ ጭምር ግብዓቱን እንዲያሟሉ ለማድረግ ይሞከራል። ግብዓቶችን በተገቢው መንገድ አለመሟላት እንዲሁም ብቁ የሆኑ መምህራንን ላለመቅጠራቸው ምክንያት ሊሆን የሚችለው ምናልባትም ለወጪ ቅነሳ ሊሆን ይችላል።

በመመሪያ ጥሰት የሚከተለውን ችግር ለመከላከል እንደ አንድ መፍትሄ የሚወሰደው ከባለድርሻ አካላቱ ጋር ተገናኝቶ ምክክር ማድረግን ነው። ችግሮቹን በጋራ እያነሱ በመወያየት መሆን የሚገባውንና መሆን የሌለበትን ማመላከት ያስፈልጋል። እንደ መንግሥት መጠየቅ የሚፈልጉትን ጠይቀው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ማድረግም ነው። ከዚህ ሂደት በኋላ ግን ተቋሙን እስከመዝጋት የሚደርስ እርምጃ መውሰድ ይሆናል። በተለይ በጤና ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች ከሰው ህይወት ጋር የተያያዘ ሥራ ላይ እንደመሰማራታቸው ተከታታይነት ያለውና ልዩ ትኩረት በመስጠት ክትትል በመደረግ ላይ ይገኛል።

2009.ም ከዚህ ጋር በተያያዘ፤ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው፣ ፕሮግራም የታገደባቸው፣ እንዲዘጉ የተደረጉ ተቋማትና በወንጀል ተጠይቀው የታሰሩና በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙ አመራሮችም እንዳሉ አልሸሸጉም። ነገር ግን ኮሌጆችን ከመዝጋት ጋር ተያይዘው የሚመጡ በርካታ ጉዳቶች ይኖራሉ። መታሰብ ያለበትም የተማሪዎችና የወላጆቻቸው ጉዳይ ነው። በመሆኑም ከእርምጃው በፊት የማረቅ ስራዎችን ማከናወን፤ ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን እስከ መዝጋት የሚደርስ እርምጃ መውሰድ ይሆናል። በቀጣይም ኤጀንሲው፤ ከፐብሊክና የሰው ኃይል ሚኒስትር፣ ከፍትህ፣ ጸጥታ እና የአስተዳደር አካላት ጋር በጋራ በመሆን ለመስራትም አቅዷል።

 

ብርሃን ፈይሳ

 

 

Published in ማህበራዊ

«ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በህጋዊ መንገድ አገር ውስጥ የሚገኝ የውጪ ዜጋ በመረጠው የአገሪቷ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከአገር የመውጣት ነፃነት አለው» የሚለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገመንግሥት ነው፡፡ ምንም እንኳ በአንቀፅ 32 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ ይህ ሀሳብ ሰፍሮ ቢገኝም፤ አሁን አሁን በዜናዎቻችን ላይ እንደሚገለፀው፤ በአንድ ክልል ያሉ የሌላ ክልል ተወላጆች ከኑሯቸው የሚፈናቀሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

የትኛው ክልል የማን ክልል ሰዎችን አስወጣ? ያስወጣው የክልሉ ህብረተሰብ ነው ወይስ የክልሉ መንግሥት? የክልል ፖሊስ ነው ወይስ የፌዴራል ፖሊስ? የሚለውን ማጣራት ስለሚያስፈልግ ይህን እንተውና በኢትዮጵያ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ መንስኤውና መፍትሄውን አስመልክቶ ምሁራን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰጡንን አስተያየት ይዘን እንነሳ፡፡

ወቅታዊው ሁኔታ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጥላሁን እንዳሻው፤ በእርግጥ ህገመንግስቱ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የአገሪቷ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት መብት እንዳለው አረጋግጦለታል፡፡ ይሁን እንጂ በተግባር ይህ በኢህአዴግ አገዛዝ እየተከበረ አይደለም፡፡ በህገመንግስቱ ብቻ ሳይሆን በአገሪቷ ብሔራዊ መዝሙርም የዜግነት ክብር እየተባለ ሃሳቡ ቢስተጋባም በተግባር ሥራ ላይ እየዋለ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡

‹‹በህገመንግስቱ አንቀፅ 51 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ ‹የፌዴራል መንግሥት ህገመንግስቱን ይጠብ ቃል፤ ያስከብራል› ይላል፡፡ ነገር ግን መንግሥት ህገመንግስቱን እያስጠበቀ አይደለም፡፡ህገመንግስቱ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ያሉበት መሆኑ ቢታወቅም፤ ከነክፍተቱም ቢሆን የፌዴራል መንግሥት ህገመንግስቱን የማስከበር ግዴታ አለበት፡፡ ዋነኛ ሥራው ፀጥታና ሰላም ማስከበር፤ ማንኛውም ዜጋ በሰላም ሰርቶ እንዲኖር ማስቻል ነው›› የሚሉት አቶ ጥላሁን፤ መንግሥት ህገመንግስቱ ላይ የተረጋገጡ የዜጎች መብቶችን የማስከበር ግዴታ እንዳለበት ሊረሳ አይገባም፡፡ አሁን ግን ዋነኛ ሥራውን ዘንግቶታል፤ ህገመንግስቱን የማስከበርና የማስፈፀም ትልቅ ሃላፊነትን የማይወጣ መንግሥት፤ መንግሥት ነኝ የማለት ብቃት የለውም ይላሉ፡፡ ልማትና እድገት የመንግሥት ተጨማሪ ሥራዎች በመሆናቸው በእነዚህ መስፈርቶች ብቻ መንግስትነቱ የተረጋገጠ ነው ሊባል እንደማይችል አብራርተዋል፡፡

‹‹በግልፅ የሌላ አገር ዜጎች ከሀገር ይውጡ በሚል እንደሚባረሩት ሁሉ፤ የአንዱ ክልል ሰው ሌላ ክልል ሄደው ሲኖሩ ግፍ እየተፈፀመባቸው ነው፡፡ አካላዊና ሞራላዊ ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ህገመንግስቱ ደግሞ ማንኛውም ዜጋ በፈለገበት የአገሪቷ አካባቢ መኖር እንደሚችል ቢያስቀምጥም ህገመንግስቱ እየተጣሰ ነው፡፡ ለፌዴራልና ለክልል መንግስታት የተሰጠው ስልጣን ተለያይቷል፡፡ በህገመንግስቱ አንቀፅ 51 እንደተቀመጠው የክልል መንግሥት የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ፖሊስ ማደራጀት ይችላል፡፡አሁን ግን ክልሎች ልዩ ሃይል ሲያደራጁ የፌዴራል መንግሥት በዝምታ ከማየት አልፎ ድጋፍ እየሰጠ ነው። የትኛውን የህገመንግስት አንቀፅ መሰረት አድርገው ክልሎች ልዩ ሰራዊት እንዲያደራጁ ባይፈቀድም፡፡ ይህ ግን በተግባር እየተፈፀመ ነው» በማለት ይናገራሉ፡፡

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አበባየሁ መሃሪ በበኩላቸው፤ በተፈለገው የአገሪቷ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የመስራት እና የመኖር መብት እየተጣሰ መሆኑ እሙን ነው ይላሉ፡፡ ከዚህ የመብት ጥሰት በተጨማሪ የተለየ አስተሳሰብ ያለው እና የገዢው ፓርቲ ተቃዋሚ ኢትዮጵያዊ በአገሩ እንዳይኖር እየተደረገ ይገኛል፡፡ ጉልበትና እውቀት ያለው ዜጋ ተወዳድሮ በፈለገበት የአገሪቷ አካባቢ ስርቶ እንዳይበላና ኑሮውን እንዳይመሰርት ያደረጉት የገዢው ፓርቲ የኢህአዴግ ካድሬዎች መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ በክልሎች እንኳን ሰው መኪና ሲያልፍ በታርጋ ቁጥሩ ተለይቶ የሚታይ መሆኑን እና በሌሎች ክልሎች የመኖርም ሆነ የመንቀሳቀስ መብት እየተጣሰ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ዲን ዶክተር ኪዳነ ግደይ በበኩላቸው፤በጉዳዩ ላይ ትክክለኛ መረጃውን ማግኘት አልተቻለም፡፡ በማህበራዊ ድረገፆችም ሆነ መደበኛ ባልሆነ መልኩ በስሚ ስሚ የሚወሩ ነገሮች እና ካለፉ በኋላ የሚቀርቡ ዜናዎች አሉ፡፡ ማንኛውም ዜጋ በየትኛውም የአገሪቷ አካባቢ ሙያውን ሽጦ ማግኘትና የመስራት መብት አለው፡፡ ይሁን አንጂ የመስራትም ሆነ የመኖር መብት እየተጣሰ መሆኑ ይገለፃል፡፡ ሆኖም የተጣራ መረጃ መስጠት ላይ ክፍተት መኖሩን ይናገራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ኮሌጅ የመንግሥትና የሰብዓዊ መብት መምህሩ ዶክተር ዘመላክ አይተነው፤ «በእርግጥ አሁን ላይ በዚህ ክልል የዚህ አገር ተወላጅ መኖር የለበትም በሚል፤ ይሄ ብሔር በተጨባጭ ተፈናቅሏል ብሎ ማረጋገጥ ቢያስቸግርም ይህንን የሚያመለክቱ ዜናዎች አሉ፡፡ ከቤንሻንጉል አማራ ይውጣ ተባለ፤ ከሶማሌ ኦሮሞ ይውጣ ተባለ፤ ከኦሮሚያም ሶማሌ ይውጣ ተባለ የሚሉ ወሬዎች እየተሰሙ ነው፡፡ ይህ እውነት ከሆነ ግልፅ ህገመንግሥትን የመጣስ ተግባር ነው» ይላሉ፡፡

የቀድሞ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እና የአሁኑ የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ክልል በነፃነት መንቀሳቀስ፤ ሰርቶ የመኖር፤ ንብረት የማፍራት እና ለንብረቱ ዋስትና የማግኘት መብት አለው፡፡ ይህ መብት መከበር እንዳለበት አያጠያይቅም ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ፅህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ሃላፊው አቶ ለጥይበሉ ሞቱማ፤ በህገመንግስቱ በአንቀፅ 32 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ እንደተቀመጠው ህገመንግስቱ ለሁሉም ዋስትና ሰጥቷል፡፡ይሁን እንጂ በማንኛውም አካባቢ የመኖር መብት የሚጣስበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው የሚለውን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ ድርጅቱ በተለያዩ ሁኔታዎች እየታየ ያለው የመፈናቀልን ጉዳይ እየለየ እና የችግሩ ፈጣሪ ማን ነው? የሚለውን እያጣራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የችግሩ ምንጭ

ዶክተር ኪዳነ የችግሩ መነሻ የክልልም ሆነ የፌዴራል መንግስቱ ክፍተት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የፌዴራል ስርዓቱ ምሰሶ የሆኑትን የብሔር ብሔረሰቦችን መብት መጠበቅ ላይ ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ ህዝቡ ችግር የለበትም፡፡ መንግሥት ችግሮችን ተከታትሎ በመለየት መፍታት ቢኖርበትም አሁን ባለው እውነታ ከላይ እስከታች ይህ እየሆነ አይደለም፡፡ ‹‹እታች ያሉ አካላት ግጭት ማስነሳት በሚፈልጉ ቡድኖች የተጠመዱ ይመስለኛል፡፡ እታች ያለው አመራር ላይ ክፍተት በመፈጠሩ ወጣቶችና ተንቀሳቃሽ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመጠቀም ብሔርን ከብሔር በማጋጨት የማቀጣጠል ሥራ እየተሰራ ይገኛል» የሚል ዕምነት አላቸው፡፡

ዶክተር ዘመላክ በበኩላቸው፤ «በኢትዮጵያ የሰዎች መብት ተከበረ፤ ዴሞክራሲ ሰፈነ የሚባለው የብሔር መብት ስለተከበረ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን መብት ይህ ማለት ብቻ አይደለም፡፡ የተለያየ አስተሳሰብና ርዕዮተዓለም ያለው፤ ካለው የፖለቲካ ሥርዓት አስተሳሰብ ውጪ የሚያስበው ሰውም መብቱ ሊከበር ይገባል፡፡ አንድ ርዕዮተዓለምና አንድ አስተሳሰብ ብቻ ከየአቅጣጫው መገፋቱ ጥሩ አይደለም፡፡ትግሬም ሆነ ኦሮሞ እንዲሁም አማራም ሆነ ሌላ የብሔር መብት ተከበረለት ተብሎ አስተሳሰቡ የማይከበርለት ከሆነ እና ህገመንግስቱ ባስቀመጠው መሰረት የሁሉም ሃሳቦች ካልተስተናገዱ ሰዎች ሃሳብን ከመወርወር ይልቅ ወጥተው ድንጋይ መወርወር ይጀምራሉ» በማለት የችግሩን ምንጭ ይናገራሉ፡፡

ሌላው ዶክተር ዘመላክ የገለፁት፤ የብሔር ግጭት የተለመደ መሆኑን ነው፡፡ አንዱ አንዱን አቅፎ እና ደግፎ ይኖራል፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ አንዱ ሌላውን ሲገፋ ማየት ተለምዷል፡፡ ቁምነገሩ አሁን ላይ በጣም ፖለቲካዊ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡ አሁን ህብረተሰቡ ውስጥ ይህ መኖሩ አይካድም፡፡ በኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔሮች፣ ሃይማኖቶች እና አስተሳሰቦች አሉ፡፡ አንድ ብሔር፣ ሃይማኖት ወይም አስተሳሰብ ብቻ የበላይ ሆነ የሚል ሃሳብ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ አስተሳሰብ መሰረት የለውም ማለት ባይቻልም፤ ዋናው የተለያየ ብሔር፣ ሃይማኖትና አስተሳሰብ እኩል ማስተናገድ ያስፈልጋል የሚለው ነው ይላሉ፡፡

አቶ ጥላሁን ከላይ በተገለፀው መሰረት ችግሩ ከህዝቡ አስተሳሰብ ጋር የተገናኘ ነው የሚለውን ሃሳብ ይቃወማሉ፡፡ «የኢትዮጵያ ህዝብ የእርስ በእርስ የጥላቻ ስሜት የለውም፡፡ ችግሩ የአገዛዙ ነው፡፡ ከከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ እስከታች ድረስ ያለው አገዛዝ ጤነኛ አይደለም፡፡ መንስኤው ይኸው ነው፡፡ ከሶማሌ ክልል ኦሮሞዎችን ያስወጣው የሶማሌ ህዝብ ሳይሆን የተደራጀው አካል ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩ ያለው ህዝቡ ውስጥ ሳይሆን አገዛዙ ላይ ነው፡፡ የህገመንግስት ጥሰቱ የሚፈፀመው በፌዴራል መንግሥት ጭምር ነው፡፡ የእዚህ ሁሉ ጉዳይ መንስኤው የትኛውም ብሔር ብሔረሰብና ህዝብ ሳይሆን አሁን ያለው አገዛዝ ነው» በማለት ነው የችግሩን ምንጭ የተናገሩት፡፡

አቶ አበባው ደግሞ፤ ግለሰቦችን የሚጎዱትና ከብሔር ጋር ተያይዞ በደሉን የሚፈፅሙት ካድሬዎች እንጂ የአንዱ ክልል ህዝብ የሌላውን ክልል ህዝብ እየጠላ አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ህዝቡ እርስ በእርሱ ተዋህዶ አንድ ሆኖ መኖር ይፈልጋል፡፡ የማንኛውም ክልል ሰው የሌላውን ክልል ተወላጅ አይጠላም፤ አያባርርም፡፡ ይህን የሚያደርጉት ታች ያሉ የገዢው ፓርቲ አባላት (ካድሬዎች) ናቸው፡፡ ህዝቡ የተጋባ አብሮ የኖረና አብሮ የበላ የተዋለደ ነው፡፡ ተዘዋውሮ የመስራት መብት ጥሰት አሁን እየታየ ያለ ሳይሆን ለ26 ዓመታት የዘለቀ፤ ከሥርዓቱ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

አቶ ለጥይበሉ ሞቱማም በበኩላቸው አሁን ለሚስተዋሉት ችግሮች መንስኤውን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሻቸው ‹‹እየተጣራ ነው፡፡›› የሚል ሲሆን መረጃ ሲገኝ አጥፊዎቹ ለህግ የሚቀርቡ ይሆናል ብለዋል፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የአሰራር ችግሮች በዜጎች ላይ ቅሬታ እየፈጠሩ እና እንደዚህ አይነት ጉዳት እያስከተሉ ነው የሚል ግምት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ ይህንን መንግሥትም በአንክሮ እየተከታተለ እና እያጣራ ይገኛል፡፡ ህገመንግስቱን ማን ጣሰው የሚለው እየተለየ ነው? በማለት «ክልሎች ከህገመንግስቱ ውጪ ሃይል እንዲያዘጋጁ ተፈቅዷል፡፡ መንግሥት ህገመንግስቱን እየጣሰ ነው» የሚለውን ሃሳብ የሚቃወሙት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ክልሎች ራሳችን መቆጣጠር አልቻልንም ካሉ የፌዴራል መንግሥቱ ህገመንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ጣልቃ የሚገባበት ሁኔታ መኖሩንም ጠቁመዋል ፡፡

የመፍትሄ ሃሳቦች

ዶክተር ኪዳነ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ላይ በስፋት መሰራት አለበት፡፡ ወጣቶች መብትና ግዴታቸውን ማወቅና ህገመንግስቱን በጥልቀት መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ በሁሉም ደረጃ ሃላፊነትን መውሰድ መለመድ አለበት፡፡ አጥፍቶ መደበቅ፤ ህዝብን እየጎዳ እና ቁርሾ ውስጥ እየከተተ፤ ይባስ ብሎ የፌዴራል ስርዓቱ ላይ አደጋ እያስከተለ በመሆኑ ጥብቅ ክትትል መደረግ አለበት፡፡ በተለይ የፌዴራል መንግሥቱ ነገሮች ሳይባባሱና ሳይበላሹ ቀድሞ መከታተልና መፍታት እንዲሁም በፍጥነት ምላሽ መስጠት ላይ መዘናጋት የለበትም፡፡

«መንግሥት የእዚህ ሁሉ የበላይ አካል ነው፡፡ ህዝብ ዋስትና ሊሰማው ይገባል፡፡ መንግሥት ይህን ማጠናከርና ጥበቃ ማድረግ አለበት፡፡ በክልልና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያለው ልዩነት ግልፅ መሆን አለበት፡፡ የስልጣን ክፍፍሉ ላይ ወጣ ገባነት አለ፡፡ ክልሎች ራሳቸውን ማስተዳደር፤ በጀታቸውን የማስተዳደር ዕድል ሲሰጣቸው፤ በክልላቸው ውስጥ ያሉ ሌሎች ብሔሮችን ማስተዳደር ላይ ክፍተት ሲኖር፤ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ መግባት በሚባል ደረጃ ባይሆንም ክትትል አድርጎ የዕርምት እርምጃ እንዲወሰድ መደረግ ይጠበቅበታል» ይላሉ፡፡

ዶክተር ኪዳነ በበኩላቸው፤የክልል መንግስታትና የፌዴራል መንግሥት ፖሊስም ሆነ ወታደርን ሲያዘጋጅ እንዴት ነው? የክልል መንግስታቱ እስከምን የዘለቀ ስልጣን አላቸው? የሚለው በደንብ ለይቶ ማስቀመጥና ህዝቡና አመራሩ እንዲያውቀው ማድረግ ይገባል፡፡ እንደዚህ አይነት ችግር ሲከሰቱ የክልል መንግስታት ሃይል ሲጠቀሙ የማባባስ ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ በተለይ የክልል ፖሊሶች በየዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ሲገቡ ትንኮሳውና የዘር ጥላቻውን የሚባባስበት ሁኔታ ስለሚፈጠር፤ ሃይል ሲያስፈልግ በትክክል ማየትና የፌዴራል መንግሥት ብቻ ሃይል መጠቀም አለበት፡፡ ከስር ከስር ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋል፡፡ የክልል ፖሊሶች የክልል ተቋማት ላይ በማተኮር፤ የፌዴራል ተቋማቱን ደግሞ የፌዴራሉ አካል ጥበቃ ቢያደርግላቸው ይመረጣል ይላሉ፡፡

ሌላው ዋነኛው መፍትሔ ህገመንግስቱን ማስጠበቅና ህብረተሰቡ እኩል ግንዛቤ እንዲኖረው ማስቻል ላይ መሰራት ነው፡፡ አሁን ላይ የሚታየው ምልክት ከባድ ነው፡፡ የኑሮ ውድነት፤ ሥራ አጥነት እና ሌሎችም ይህንን የሚያባብሱ ነገሮች በመኖራቸው ችግሮቹን ከስር መሰረት መንቀል ያስፈልጋል፡፡ የተንቀለቀለውን ዕሳት ማጥፋት ብቻ ሳይሆን፤ ዕሳቱን የሚያስነሱና የሚያቀጣጥሉ ክብሪቶችን ለመቀነስና ከተቻለም ለማጥፋት ቀድሞ መስራት ይገባል ይላሉ፡፡

ዶክተር ዘመላክ መንስኤው የፌዴራል ስርዓቱ ነው ከተባለ መፍትሔው ከባድ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ «የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የአፋር ወይም የሌላ ክልልን እናፍርሰው ቢባል አይቻልም፡፡ ሰው የክልሉን ካርታ፣ ባንዲራውን ያውቃል፡፡ ስለዚህ እሺ አይልም፡፡ በተቃራኒው እነዚህ ሰዎች ሊከፋፍሉንና ሊያዳክሙን ነው የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ ስለዚህ ወደ ኋላ እንመለስ ማለት ነገሮችን ከማስተካከል ይልቅ ሌላ ችግር ይፈጥራል ብዬ እሰጋለሁ» ከዚህ አንፃር መፍትሔው የአስተሳሰብ ብዝሃነትን ማስተናገድ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

መፍትሔው የረዥምና የአጭር ጊዜ ዕቅድ በመያዝ ነገሮችን የሚያባብሱ ነገሮችን ማቃለል ነው፡፡ ሰው ስሜታዊ እየሆነ በመምጣቱ እና ትንሿ ጉዳይ እየገነነች የምትመጣ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት የሚወሰዱ መፍትሔዎች በጣም ታስቦባቸውና የሰውን ስሜት በማይነኩና ቅሬታ በማይፈጥሩ መልኩ ቢደረጉ ጥሩ ነው ይላሉ። ህገመንግስቱን እና ህጉን በመጠቀም ችግሩን መፍታት የሁሉም ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ ከሁሉም በላይ የረዥም ጊዜ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በህገመንግስቱ መግቢያ ላይ የተቀመጠው አንድ የኢኮኖሚክ ማህበረሰብ እንገነባለን ብሎ ተስፋ ያደርጋል፡፡ ይህ የሚሆነው ሁሉም በያለበት ሳጥን ታጥሮ ሳይሆን አንዱ ከሌላው ጋር ግንኙነት መፍጠር ሲችል ነው፡፡ ይህ መሆን የሚችለው ደግሞ አንዱ ከራሱ ወደ ሌላው ክልል ተዘዋውሮ በስራም ሆነ በማህበራዊ ግንኙነት መቆራኘት ሲችል መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የፌዴራል ስርዓቱ እንዳለ ሆነ በክልሎች ውስጥ ያለ የተለያየ አስተሳሰብ የሚስተናገድበት ሁኔታ መመቻቸት ይኖርበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዋ ሌላ መሆን ነበረበት ብሎ የሚያምን ግለሰብና ቡድን ይኖራል፡፡ የእነርሱንም መብት ማክበር ያስፈልጋል፡፡ የተነጠሉ ቡድኖችን ለማካተት እና መብታቸው የተጣሱ ሰዎችን መብት ለማስከበር የአሁኑ ህገመንግስት አያንስም፡፡ ስለዚህ ህጎችን በትክክል በሁሉም ሰዎች ላይ መተግበር አለበት፡፡ ለእዚህ ደግሞ ህገመንግስቱ ዝግ አይደለም፡፡ ህገመንግስቱ ላይ ያሉ ከነፃነት፣ ከዴሞክራሲ፣ ከምርጫ፣ ሃሳብን በነፃነት ከመግለፅ፤ ከሰብዓዊ መብት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በትክክል በህገመንግስቱ መሰረት ቢከበሩ ችግሮች እንደማይደራረቡ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ዋናው መፍትሔ የተለያዩ ሃሳቦች የሚስተናገዱበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ቅስቀሳዎችም ሆነ ፖለቲካዊ ተሳትፎዎች በነፃነት መካሄድ ካልቻሉ ነገሮቹ ለጊዜው በሚወሰዱ ርምጃዎች ቢበርዱም ቆይተው ተመልሰው መከሰታቸው ስለማይቀር፤አ መጣጡም ከዚህ በከፋ መልኩ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡

ዶክተር ዘመላክ በበኩላቸው፤ ሌላው ቀርቶ የፌዴራል ሥርዓቱ መፍረስ አለበት ሊል የሚችል ይኖራል፡፡ ሥርዓቱ አይደለም አፈፃፀም ላይ ያለ ችግር ነው የሚልም ይኖራል፡፡ በማለት እርሳቸው ግን የፌዴራል ስርዓቱ በዚህ ምክንያት መሻሻል አለበት ማለት ቢያዳግታቸውም ዋናው ቁምነገር ህገመንግስቱ ከተተገበረ ችግሩ ይፈታል ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ፡፡

ህገመንግስቱ ራሱ ላይ በተቀመጠው የማሻሻያ ህግ መሰረት መሻሻል ይቻላል፡፡ ህገመንግስቱ በትክክል የሚተገበርበት ሁኔታ ቢፈጠር የተሻለ ነገር ይመጣል፡፡ ህገመንግስቱን እየጣሰ ያለው ማን ነው? ከተባለ ሁሉም እየጣሰው ነው፡፡ ችግሩ መንግሥት ህገመንግስቱን ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበር የሠራው ሥራ ውስን ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም መነሻቸውም ሆነ መድረሻቸው ህገመንግስቱ መሆን አለበት ብለው እንደሚያምኑ ይገልፃሉ፡፡

አቶ ጥላሁን ደግሞ መፍትሔው ፓርቲው ራሱን መለወጥ አለበት፡፡ አለበለዚያ ህገመንግስታዊ መብቶችን የማስከበር የመምረጥ የመመረጥ፤ ሃብት የማፍራት፤ ዜጋ እንደዜግነቱ መብቱን ማስከበር አለመቻሉን አምኖ እና ሃላፊነት ወስዶ ኢህአዴግ ከስልጣን መልቀቅ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የሁሉንም ህዝብ ተከባብሮ የመኖር ፍላጎትን የሚያራምድ መንግሥት እንዲያቋቁም መፍቀድ ይገባዋል ይላሉ፡፡

ፕሮፌሰር ፍቃዱ ግን እንደአቶ ጥላሁን ፓርቲው ይልቀቅ ከማለት ይልቅ መፍትሔው፤ የሌላውን መብት የጣሰ አካል ተጠያቂ ማድረግ ነው ይላሉ፡፡ በቅድሚያ ማስተማር፤ ችግር የፈጠሩትን መጠየቅ ይገባል፡፡ አገሪቷ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበች በመሆኑ፤ አልፎ አልፎ በሚከሰቱ ችግሮች ከመደናገጥ ይልቅ ተከታትሎ ችግሩን መፍታት ያስፈልጋል፤ ይህ ከሆነ ችግሩ ቀላል ይሆናል የሚል ዕምነት አላቸው፡፡

አቶ ለጥይበሉ በበኩላቸው፤ የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት አባባሽ ምክንያቶች ናቸው በሚል የተገለፀውን ሃሳብ ይቃወማሉ፡፡ ኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት ምንም እንኳ በሚፈለገው ልክ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ማለት ባይችልም፤ በዚህ ደረጃ ለሚፈጠሩ ችግሮች ከሚጠቀሱ መንስኤዎች ውስጥ አንደኛው ሥራ አጥነት ነው ብለው እንደማያምኑ ይገልፃሉ፡፡ የኑሮ ውድነቱም ቢሆን አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች የሚፈጥሩት በመሆኑ፤ በሚፈለገው ደረጃ እየተሰራ ባይሆንም ይህኛውም እንደምክንያት የሚጠቀስ አለመሆኑን ያመለክታሉ፡፡ መልካም አስተዳደር ላይም የህዝብ እርካታ ባይረጋገጥም ችግሩን ለማቃለል ሥራ እየተሰራና ለውጦች እየታዩ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። እነዚህ ጉዳዮች አባባሾች ናቸው በሚል የተሰጠውን አስተያየት ይቃወማሉ፡፡ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች መነሻቸውን በመጣራት ላይ መሆኑን ለአብነት በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች የተፈጠሩት ግጭቶች መነሻቸው ለ11 ዓመታት ተንከባለው የመጡና በጊዜ ያልተቋጩ ጉዳዮች መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡

ስጋቶች

ብዙዎቹ አስተያየት ሰጪዎች ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፤ ዶክተር ኪዳነ በዚሁ ከቀጠለ ከፍተኛ ስጋት እንዳለባቸው ሲገልፁ፤ ዶክተር ዘመላክ ደግሞ ጉዳዩ ምልክት ነው፡፡ ከፍተኛ ህመምን እንደሚጠቁመው ራስ ምታት መታየት አለበት፡፡ ትልቅ ችግር መኖሩን የሚያሳይ በመሆኑ በህገመንግስቱ መግቢያ የተቀመጠው አንድ ማህበረሰብ የመፍጠሩ ተስፋ ይጨልማል ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል፡፡

አዝማሚያው አደገኛ በመሆኑ፤ አንዱ ሌላውን ሲያስወጣ በበቀል የሚነሳ አካል ተበራክቶ ወደ ማያቋርጥ ግጭት ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ከፍተኛ ስጋት እንዳላቸው ያመለክታሉ፡፡ አቶ ጥላሁንም አደጋው የከፋ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን አቶ ለጥይበሉ በበኩላቸው፤ መንግሥትም የጉዳዩን ክብደት ተረድቶ በትኩረት እየተከታተለና እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወደፊት እየተፈጠሩ ያሉት ችግሮች በእርግጥም ቀላል አለመሆናቸውን ፓርቲያቸው የተገነዘበው መሆኑን በማመልከት፤ በእርግጥም ችግሩ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ አልነበረበትም፡፡ ችግሮች ከስር ከስር መፈታት ነበረባቸው፡፡ አሁንም ግን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ይናገራሉ። አያይዘውም ሥራዎች እየተሰሩ በመሆናቸው ወደ ፊት ችግሮች ይቃለላሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

 

ምህረት ሞገስ

Published in ፖለቲካ

በሀገሪቱ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና የተሻለ አፈፃፀም ይኖረው ዘንድ መንግሥት ከጊዜ ወደጊዜ ካጋጠሙ ችግሮች እየተነሳ መፍትሄ እያስቀመጠ በመስራት ላይ ነው። ከእነዚህ ተግባራት መካከል ሥራን ለተለያዩ ክፍሎች ማከፋፈል አንዱና ተጠቃሹ ነው። በዚህም ለአብነት የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ሥራን በሃላፊነት የሚመራ ሚኒስቴር ተቋቁሞ ወደ ሥራ ተግብቷል።

ሚኒስቴሩም ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችሉትን በርካታ ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል። በተለይም በእንስሳት ልየታና መሰል ተግባራት ዙሪያ አሰራርን ከማዘመን ጀምሮ ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ረገድ የሀገሪቱን የውጪ ገቢ ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ መንገዶችን ቀይሶ እየሰራ ይገኛል። እኛም ለዛሬ ከእንስሳትና ዓሣ ሀብት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንዲህ አጠናቅረነዋል።

ስለሚኒስቴሩ በጥቂቱ

ሚኒስቴሩ የግብርናው አንዱ ዘርፍ በመሆኑ ፤ ትልቅ ኃላፊነት የሚጠበቅበት እንደሆነ ይታመናል። በመሆኑም ግቡን ሊመታ የሚችልባቸውን አሰራሮች ቀይሷል፡፡ የህዝብ ክንፍን በማጠናከር በእያንዳንዱ ሥራው እስከታች ድረስ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል እያሳተፈና ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በሀገሪቱ የእንስሳትና ዓሳ ዕምቅ ሀብት፤ እንዲሁም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ህብረተሰብ መገንባት ላይ በሰፊው በመስራት ላይ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ምርትና ምርታማነትን ማሻሻል እና ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ የሚውል አቅርቦትን በማሳደግ ረገድ ኢኮኖሚው ላይ የራሱን አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንዲያበረክት እየተደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም ዘመናዊ የእንስሳት ኢንዱስትሪ በመገንባት ኢትዮጵያን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ፤ በአፍሪካ ቀዳሚና ተመራጭ በማድረግ በእንስሳትና ዓሣ ሀብት ምርቷ የህብረተሰቡ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በመስራት ላይ ነው፡፡

የዘንድሮ ዕቅድ ሲዳሰስ

በተያዘው በጀት ዓመት ከመንግሥት እና ከአጋር ድርጅቶች 1 ቢሊየን 90 ሚሊየን 842 ሺህ 290 ብር ተመድቧል። ይህንንም በተገቢው መንገድ ለለውጥ ለማዋል እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ በተጨማሪም መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ቅንጅታዊ አሰራሮችን በመዘርጋት የተለያዩ ድጋፎችን የማሰባሰብ ሥራ ይሰራል፡፡

በዚህም የእንስሳትና ዓሳ ምርትና ምርታማነት በዓይነት፣ በጥራትና በመጠን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጓል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጥራቱ የተረጋገጠ የእንስሳትና ዓሳ ጤና፣ ግብዓትና ምርት ጥራት ቁጥጥር ማድረግ፤ እንዲሁም የእንስሳትና ዓሳ ምርት፤ ተዋፅኦና ግብዓት ግብይትን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ በትኩረት ለመስራት ታቅዷል።በዓመቱም 23 ሚሊየን 495 ሺህ 713 የህብረተሰብ ክፍሎችን ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግም እቅድ ተይዟል።

በእያንዳንዱ ተግባር ህብረተሰቡን ከቀድሞው በላቀ ሁኔታ ተሳታፊነቱን እና ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት የሰጠው ዕቅዱ፤ ባለፈው በጀት ዓመት ሲሰራ የነበረው የእንስሳት መለያ አሰራርን አጠናክሮ ቀጥሏል። የመለያዎች አጠቃቀም ስርዓት መሰረት በሁሉም የትግበራ ጣቢያዎች (በአዳማ፣ በሚሌ፣ በጅግጅጋ፣ በመቀሌ ኳራንቲን ጣቢያዎች) ወጥነት ያለው እና ጠንካራ አተገባበር እንዲኖር በማድረግ ላይ ነው፡፡ በሚከናወኑ ሥራዎችም ውጤት ለማምጣት እርስ በእርስ የማስተሳሰር ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በዚህም በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ በርካታ ምርቶችን እሴት በመጨመር ማቅረብና ከፍተኛ የውጪ ገቢ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ዕቅዱ ሀገሪቱ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የምትሰራውን ሥራ ይደግፋል፡፡ በዚህም የማይበገር የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ለማስፋፋት፤የእንስሳት ቁጥር፣ ከመኖ ልማትና ግጦሽ ጋር ማጣጣም፤ የእርባታ ስርዓቱ ገበያ ተኮር እንዲሆን ማድረግና ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት መቀነስ፤ ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ውሀን መሰረት ያደረገ የመኖ ልማት ሥራዎች ማጠናከር፤ አርሶአደሩ ሰንባች የመኖ ተክሎችን በማልማት የመኖ ምርቱን እንዲጨምር ለማድረግ ይሰራል።

አረንጓዴ የእንስሳት ሀብት ልማት በማረጋገጥ ረገድ የግጦሽ መሬት፣ የውሀ አካላት ብክለትና ጉዳትን መከላከልና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማትን የማረጋገጥ አገራዊ ስትራቴጂን ተግባራዊ ያደረጋል፡፡

ከአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ዙሪያ የሚተገበሩ ስራዎችም የውሀ አካላት ብክለትና ጉዳትን መከላከል፤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማትን ማረጋገጥ፤ ለዓሣ መራቢያ የሆኑና የተጎዱ የሀይቅ ዳርቻ ደኖች እንዲያገግሙ እና እንዲጠበቁ ማድረግ፤ የአፈር መከላትን አንዲቀንስና ሌሎች ብክለቶች እንዳይከሰቱ ማድረግ፤ በአሁኑ ወቅት በጣና ሀይቅ እየተስፋፋ ያለው የውሀ አረም በራሱና በሌሎች የውሃ አካላት እንዳይስፋፋ ከክልል ቢሮዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ይሰራል፡፡

የተከናወኑ ተግባራት

ሀገሪቱ በርካታ የእንስሳት ቁጥር ያላት በመሆኑ ያሉትን ኢኮኖሚያዊ ችግሮችና ይህን ተከትለው ሊመጡ የሚችሉ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ለማቃለል ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ነው። ከዘርፉ የላቀ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ እንደ ትልቅ ስኬት የሚታየውም ቀድሞ ከእንስሳት ርቢ ጋር ተያይዞ የነበረውን ተለምዷዊ አሰራር በማስቀረት በምርትና በወጪ ገቢ ንግድ ላይ ለውጥ የሚያመጣ ፖሊሲ ፀድቋል፡፡ ፖሊሲውንም መሰረት አድርገው በቀጣይ ስድስት ስትራቴጂዎችና ሌሎች ደንብና መመሪያዎች ለማውጣት በሂደት ላይ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም ፖሊሲው ምርምር ላይ ያለውን ሥራ የሚያሰፋ በመሆኑ ኢንስቲትዩት ይከፈታል፡፡ በወተት፣በሥጋ፣በዶሮ እና ዓሳ ሀብት ልማት የህብረተሰብ ተሳትፎ ከመጨመር ባለፈ አባወራ እና እማወራዎች ብሎም የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማሳደግ፤ እንዲሁም ከዝርያ ማሻሻል ጋር በተያያዘም በዶሮ ፣በጋማ ከብት ዝርያ ላይ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በዚህም በሁሉም ዘርፎች ከምርትና ምርታማነት ማሳደግ ጀምሮ የወጪ ገቢም ላይ ለውጥ ሊታይ ችሏል፡፡በእያንዳንዱ ተግባርም ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር፣ምርታማነቱን ለማሳደግ እንዲሁም ምርቱ ገበያ ተኮር እንዲሆንና የተሻለ ገቢ እንዲያስገኝ ትስስር ተፈጥሯል፡፡

በዓለም ገበያ ተወዳዳሪነት ላይ ጉልህ ሚና የሚጫወተው የእንስሳት ልየታ ስራም በትኩረት ሲከናወን ቆይቷል፡፡ በዚህም ጠንካራ የክትትል ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ የተቀባይ አገራትን የእንስሳት ጤንነትና ደህንነት ፍላጎት ማሟላቱን በመመርመርና በመቆጣጠር፤ ብሎም የተለያዩ ዝርያ ማሻሻያዎችን በማድረግ የተቀባይ አገራትን እምነት ከፍ አድርጓል።ደረጃና ጥራቱን የጠበቀ እንስሳት በማቅረብ ገቢን ከፍ ለማድረግ ተችሏል፡፡

ስራዎች ሲሰሩ የተለያዩ ማነቆዎች አይጠፉምና ስጋትን መሰረት ያደረገና የተጠናከረ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ሥርዓት በማጎልበት በእንስሳት ላይ የሚደርስ ጉዳት በመቀነስ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል፡፡ በተንቀሳቃሽ ስልክ በመታገዝ ፈጣን የእንስሳት በሽታዎች ክስተት መረጃ ልውውጥ ላይ እየተሰራ ሲሆን፤ በሽታዎች በተከሰቱበት ቅጽበት ሪፖርት በማድረግ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል በተንቀሳቃሽ ስልክ የተመሠረተ ሥርዓት ተጀምሯል፡፡ በዘርፉ የሚጠበቀውን ስኬት ለማስመዝገብ ዘርፈ በዙ ተግባራት ቢከናወኑም፤ የህገወጥ ንግዱ መስፋፋት ለውጡ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደሩ አልቀረም፡፡

ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች

ዘርፉ በአሁኑ ወቅት የሚታዩትን መልካም ጅማሮዎች ለማስቀጠልና ችግሮችን ለማቃለል በሚደረገው ሂደት ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተለይተዋል፡፡ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት የቁም እንስሳት፣የአንድ ቀን ጫጩት፣ ሴመን (አባላዘር) እንዲሁም በሽታና ሌሎች የዘረመል ችግሮች ተሸክመው ወደ አገር ሊገቡ ስለሚችሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የስጋት ዳሰሳና ፍተሻ ይደረጋል። የአገር ውስጥ እንስሳትና ዓሣ ሀብትን ለመጠበቅና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች በመሆናቸው ተለይቷል፡፡የቁም እንስሳትና ቆዳና ሌጦ ግብይት ስርዓት፣ የህገወጥ ንግድ ችግርን ለማቃለል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ታቅዷል፡፡

 

ፍዮሪ ተወልደ

 

Published in ኢኮኖሚ

 

በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የሚከናወኑ ተግባራት የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በድረ ገጾቻቸው ይዘግባሉ። በተለይም በኢኮኖሚው መስክ እየታየ ያለው ለውጥ፣ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በማከናወን ላይ ያሉት ተግባራት፤ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው ለመውጣት የሚያስችላቸውን አቅጣጫ እንደያዙ፤ እንዲሁም በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች መጠናከር ላይ ትኩረት በማድረግ ዘገባዎቹ የሚዳስሷቸው እውነታዎች ናቸው።ባለፈው ሳምንት በዓለም ሚዲያዎች ትኩረት ካገኙና ለንባብ ከበቁት መካከል፤ ግብጽ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚመክር የአፍሪካ አማላጅ ቡድን ልትፈጥር ነው ስለመባሉ፤ ኢትዮጵያ ስደተኞችን በተሻለ ለማስተናገድ የሚያስችል ጥረቶችን እያከናወነች ስለመሆኑ፤ የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ አዲስ ስትራቴጂካዊ እቅድ ይፋ ስለማድረጉና ሌሎችም ይገኙበታል።

ግብጽ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚመክር የአፍሪካ አማላጅ ቡድን ልትፈጥር ነው ተባለ

ግብጽ በአባይ ግድብ ያላትን አቋም የሚገልጽላት የአፍሪካ አማላጅ ቡድን ለመፍጠር በመንቀሳቀስ ላይ መሆኗ ተገለጸ፡፡ የግብጽ ጋዜጣ አል ሾሩክ አማላጅ ቡድኑ ከአፍሪካ አጋር አገሮች ጋር በመስራት በኢትዮጵያ ግድብ ፕሮጀክት ላይ በሚፈጠረው የውሃ ግጭት የሚቆጣጠር መሆኑን ዘግቧል፡፡

ጋዜጣው ዋቢ በማድረግ ሚድል ኢስት ሞኒተር ድረገጽ እንዳስነበበው ኢትዮጵያ ለአንድ ደቂቃም ቢሆን የግድቡን ግንባታ እንደማታቆም፣ የተፈጥሮ ሃብቷ (ውሃ) መጠቀም መብቷ እንደሆነና ግድቡ ድህነትን ለማስወገድ እንደምትጠቀምበት የኢትዮጵያ የውሃ ኤሌክትሪክና መስኖ ሚኒስትር መናገራቸውን አስታውሷል፡፡

የግብጽ የውሃ ባለሙያዎች ግድቡ የአገራቸው የውሃ መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል በሚል ስጋት እንደገባቸው ጠቅሶ፣ ኢትዮጵያ ግድቡ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ስለምታውለው በተፋሰሱ ሀገራት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አለመኖሩን ስትገልጽ መቆየቷምን ጠቅሷል፡፡ የዓረብ የውሃ ምክርቤት ፕሬዚዳንት መሐሙድ አቡ ዘይድ ኢትዮጵያ አጓራባች አገሮች ሳታማክር የግድቡ ፕሮጀክት መገደቧ ከዓለም አቀፉ የውሃ አስተዳደር ህግ ጋር የሚጣረስ ነው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ እ..አ በ2011 ግንባታው የተጀመረው ግድቡ ከ70 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ችግር በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ተብሎ የሚታመንበት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ብሏል ዘገባው፡፡ ድረገጹ አክሎም ግድቡ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ግዙፉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ሲሆን፤ የግድቡ ግንባታ ወጪም ከ4ነጥብ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑ አስታውቋል፡፡

Middle East Monitor 29

November 2017

ኢትዮጵያ ስደተኞችን በተሻለ ለማስተናገድ የሚያስችል ጥረቶችን እያከናወነች ነው

የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገሪቱ ለሚገኙ ስደተኞችን ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታቸውን የሚለውጥ አጠቃላይ የስደተኞች ምላሽ ማዕቀፍ (CRRF) መክፈቱን ይፋ አደረገ፡፡ በሀገሪቱ በቅርቡ የተጀመረው የህዝብ ቆጠራ ፕሮግራም ጨምሮ በአዲሱ ማዕቀፉ በሀገሪቱ በሚገኙ 26 የስደተኞች ካምፖች ከሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያና ኤርትራ የመጡ 890ሺ ስደተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ሪሊፍ ዌብ ድረገጽ አስታወቀ፡፡

አጠቃላይ የስደተኞች ምላሽ ማዕቀፍ በአዲስ አበባ ከተባበሩት መንግሥታትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅት ተወካዮች ጋር በመሆን የተከፈተ ሲሆን፣ የሀገሪቱ መንግሥት በስደተኞች ላይ የማህበረ ቁጠባዊ ማሻሻያዎችን ለማምጣት የሚረዳ እንደ ትምህርት፣ ስልጠናና የሥራ ዕድል አጋጣሚዎች የማስፋፋት እቅዱ አካል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍጹም አረጋ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በመገንባት ላይ ያሉ ሦስት ኢንዱስትሪ ፓርኮች በዋናነት ለስደተኞች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ለመርዳት ልዩ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሦስቱም በመገንባት ላይ ያሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለግንባታቸው የሚውል 500ሚሊዮን ዶላር የተገኘው ከእንግሊዝ፣ አውሮፓ ህብረትና ዓለም ባንክ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ለ100ሺ ሰዎች ከዚህም 30ሺ ለስደተኞች 70ሺ ደግሞ ለሀገሪቱ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ የሚውል ነው፡፡

ሀገሪቱ ቅድሚያ ለአጠቃላይ የስደተኞች ምላሽ ማዕቀፍ (CRRF) በመስጠት በሀገሪቱ ለሚገኙ ስደተኞች የወሳኝ ኩነት ምዝገባ (ህዝብ ቆጠራ) ለማካሄድ የሚያስችል ፕሮግራም መክፈቷ ይታወቃል፡፡

የወሳኝ ኩነት ምዝገባው ባለፉት ዓመታት ያልታየ የመጀመሪያና ታሪካዊ የሆነ በአገሪቱ ለሚገኙ ስደተኞች ከለላ የሚሰጥ ክስተት መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ሪፖርት ገልጿል፡፡ ከዚህ በፊት በሀገሪቱ ከ70ሺ በላይ ህጻናት የተወለዱ ሲሆን፣ የልደት ምስክር ወረቀት (ሰርተፊኬት) ስለሌላቸው አሁን በቅርቡ እንደሚሰጣቸው የድርጅቱ ሪፖርት ያመላክታል፡፡

Relief Web 29 November 2017

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ አዲስ ስትራቴጂካዊ እቅድ ይፋ አደረገ

የዓለም ባንክ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ለሚያከናውናቸው የተግባር እቅድና ሀገሪቱን ለመደገፍ የሚያስችለው ስትራቴጂካዊ እቅድ ይፋ ማድረጉን ዢንዋ ድረገጽ ገልጿል፡፡ አዲሱ ለኢትዮጵያ ይፋ የተደረገው የባንኩ ስትራቴጂካዊ እቅድ እ..አ ከሚቀጥለው 2018 እስከ 2022 ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፤ ይህም ከሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ጋር የሚዛመድ መሆኑን ድረገጹ አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ካሮላይን ተርክ የባንኩ ቀዳሚ ትኩረት በሀገሪቱ መዋቅራዊና ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን በተጠናከረ ምርታማነት ማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ውጤታማ መዋቅራዊና ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ቀደም ሲል የተመዘገበውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሊያስቀጥል የሚችል፣ ምርታማነትን ከፍ በማድረግ እንዲሁም ዘላቂ የመሰረተ ልማት ፋይናንስ የማድረግ መፍትሔዎችን ለማምጣት ተወዳዳሪነትን የሚፈጥር ሊሆን እንደሚችል ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት እያደረገ ያለው ችግሮችን የመቋቋምና ሁሉን አቀፍ፣ ተቋማዊ ተጠያቂነትና ሙስናን የመጋፈጥ ጥረቶች ለመደገፍ ባንኩ በስትራቴጂክ እቅዱ ጋር ያካተተው ዋናው ዓላማው ነው፡፡ መንግሥት የተለያዩ የአሰራሩ መረጃ ማግኛ ዘዴዎች በአካባቢው አገልግሎቶችን በግልፅ ቢዘረጋም አሁንም ተጨማሪ ግልጽነት እንደሚያስፈልገው ዳይሬክተሯ አክለዋል፡፡ አገሪቱ እ..አ በ2025 ዝቅተኛው መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር እንደምትሆንና እዚህ ላይ ለመድረስም ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ እንደሚያግዛት ድረገጹ ዘግቧል፡፡

Xinhua 29 November 2017

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በክርስቲያኑ ዓለም ከፍተኛ ቦታ አለው ተባለ

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ውጭ ካሉ አገራት ከፍተኛ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ያላት ሀገር ስትሆን አማኞቹ ለእምነታቸው ያላቸው ቁርጠኝነት ከሌሎች አገራት ባሉት የእምነቱ ተከታዮች በጣም የላቀ መሆኑን ፔው ሪሰርች ድረገጽ ይፋ አደረገ፡፡ ድረገጹ ኢትዮጵያ 36 ሚሊዮን የኦርቶዶክስ ክርስቲያን እምነት ተከታይ ያላት በዓለም ከሩሲያ ቀጥላ ሁለተኛ አገር መሆኗን ጠቅሷል፡፡

ድረገጹ ባደረገው ጥናት በ13 የመካከለኛና ምስራቅ አውሮፓ አገራት የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች 34 በመቶ ሃይማኖት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሲገልጹ፤ የኢትዮጵያ የእምነቱ ተከታዮች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ማለትም 98 በመቶ ሃይማኖት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግሯል፡፡

በአለባበስም ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች 93 በመቶ የሃይማኖታዊ አለባበስ የሚከተሉ ሲሆን፤ በተመሳሳይ የምስራቁና መካከለኛ አውሮፓውያኑ 64 በመቶ እንዲሁም ኢትዮጵያውያኑ 89 በመቶ በእግዚአብሔር ፍጹምነት ሲያምኑ አውሮፓውያኑ 56 በመቶ መሆናቸው አብራርቷል፡፡

በጾም ጊዜያትም ኢትዮጵያውያኑ 87 በመቶ የሚጾሙ ሲሆን፤ አውሮፓውያኑ ግን 27 በመቶ እንዲሁም ለቤተክርስቲያኒቱ አስራት በመክፈል ኢትዮጵያውያን 57 በመቶ አውሮፓውያኑ 14 በመቶ መሆናቸው ጠቁሟል፡፡

ጥናቱ እንዳረጋገጠው፤ ኢትዮጵያውያን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ከሌሎቹ በይበልጥ በማህበራዊ ህይወት አክራሪዎች እንዲሁም በተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ፣ ዝሙት፣ ጽንስ ማቋረጥ፣ ፍቺና አልኮላዊ መጠጥ በከፍተኛ የሚቃወሙ ናቸው፡፡

Pew research 28 November 2017

ታላቁ የህዳሴ ግድብ በግብጽ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አለመኖሩን ተገለጸ

በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር ታየ አጽቀስላሴ በካይሮ ከአፍሪካ ጉዳዮች ኮሚቴ ጋር ባደረጉት ውይይት ታላቁ የህዳሴ ግድብ በግብጽ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አለመኖሩን መናገራቸው ኢጂፕት ኢንዲፐንደንት ድረገጽ ገለጸ፡፡ በተጨማሪም አምባሳደሩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በታኀሣሥ አጋማሽ በግብጽ ጉብኝት በማድረግ በአገሪቱ ፓርላማ ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡

በግድቡ ግንባታ ዙሪያ አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ከግብጽና ሱዳን ጋር ያላት የመወያየት መድረክ እንደምትቀጥልበት ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ ጉዳዮች ኮሚቴ አባል ሃተም ባቻት አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ግብጽን እንደማትጎዳ አረጋግጠዋል ብለዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት የሱዳን ውሃ ሚኒስትር ኢትዮጵያና ሱዳን በግድቡ ዙሪያ ለመወያየት ግብጽን እየጠበቁ መሆኑን መናገራቸውም ድረገጹ ጠቅሷል፡፡

ግብጽ በበኩሏ፤ ኢትዮጵያ በግብጽ የሚደርሰው የውሃ መጠን በግድቡ ምክንያት እንዳይቀንስ በሚለው ድርድር ለመሳተፍ ፈቃደኛ አለመሆኗን ዘገባው ይጠቅሳል፡፡ የኢትዮጵያ ውሃ፣ ኤሌክትሪክና መስኖ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግብጽ ከምታደርገው ታቃውሞ ባሻገር ግድቡን ከመገደብ የሚያስቆማት አንዳች ነገር እንደሌለ መናገራቸው ድረገጹ አክሏል፡፡

Egypt independent November 28, 2017

የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ አስደናቂ ነው ተባለ

እውቅናው ከዓመት ዓመት እያደገ የመጣው ታላቁ ሩጫ በዘንድሮው 17ኛው ፕሮግራሙ ከውጭ አገራት በመጡ አትሌቶችና ተሳታፊዎች አድናቆት ማትረፉን ኤክስፕረስ ኤንድ ስታር ድረገጽ አስታወቀ፡፡ ድረገጹ 60ኛው የልደት ዓመቱን በማክበር በታላቁ ሩጫ የተሳተፈው ዓይነ ስውሩ ዴቭ ሄሌይን በመጥቀስ የዘንድሮ ታላቁ ሩጫ ለየት ያለና የሀገር ውስጥና የውጭ ታዋቂ አትሌቶችን ጨምሮ 44ሺ ተሳታፊዎች የተገኙበት ልዩ አጋጣሚ መሆኑን ገልጿል፡፡

17ኛው የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫው 10ኪሜ ርቀት የሸፈነና ለዴቭ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈበት እጅግ ማራኪና አስደናቂ ክስተት ያገኘበት ሆኖ አግኝቶታል፡፡ ዴቭ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት 25 የታላቁ ሩጫ ውድድሮች ተሳትፎ 250 ማይሎችን የሸፈነ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ የመጨረሻውና በጣም አስደናቂ የሆነ ታሪካዊ ክስተት ያገኘበት መሆኑን ይናገራል፡፡

ዴቭ በታላቁ ሩጫ የማይረሳ ትውስታ ካስገኙለት በጎዳናው የነበረው የሰዎች መዝናናት ሙዚቃና ዳንስ ከሁሉም በላይ ማራኪ ነበር ይላል፡፡ በአዲስ አበባ የተካሄደው ታላቁ ሩጫ በ8ሺ ጫማ ከባህር ወለል ከፍታ ሲሆን ዓይነ ስውሩ ዴቭ ውድድሩን በደጋፊዎቹ በመታገዝ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ችሏል፡፡ ዴቭ ብርቱ አትሌት ሲሆን በቅርቡ የዴስ ሳብለስ ማራቶን ያጠናቀቀ የመጀመሪያው ዓይነ ስውር አትሌት ነው፡፡

Express and star 28

November 2017

 

በሞኒተሪንግ ክፍል

 

 

Published in ዓለም አቀፍ
Monday, 04 December 2017 20:15

አፋር ሰመራ ላይ

 

«በሕገ መንግሥታችን የደመቀ ሕብረ ብሔረተኝነታችን ለሕዳሴአችን» በሚል መሪ ቃል ለ12ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ኅዳር 29 ቀን 2010 .ም በአፋር ሰመራ ከተማ ሊከበር ዝግጅቱ ተጠናቋል። የአገራችን ህገ መንግሥት የፀደቀበት ዕለት ኅዳር 29 ቀን 1987 .ም ምክንያት በማድረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሦስተኛው የፓርላማ ዘመን አንደኛ ዓመት የሥራ ጊዜ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ሚያዝያ 21 ቀን 1998 .ም ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት በኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ምክንያት የሆነው ሕገመንግሥት የፀደቀበት ቀን (ኅዳር 29) የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በየዓመቱ በተለያዩ ዝግጅቶችና ዘላቂ የልማት ሥራዎች እንዲከበር ተደርጓል።

ስያሜው «የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን» ይባል እንጂ የምናከብረው ህገ መንግሥታችን የፀደቀበት ቀን ነው። ሕገ-መንግሥት የፀደቀበት ቀን ደግሞ በማንኛውም አገር ይከበራል። በእኛም አገር መከበሩ ሕጋዊ ነው። በዚህ መነሻ ከኅዳር 29 ቀን 1999 .ም ጀምሮ በምክር ቤቱ አስተባባሪነት፤ በተለያዩ ክልሎች አስተናጋጅነት የሕዝቦች ተከባብሮና ተቻችሎ መኖር በሚገልጽና ለአንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓትን ለማምጣት በሚያስችል መልኩ ይከበራል።

እስካሁን ድረስ ለ11 ጊዜያት ተከብሯል። የአሁኑ በአፋር ሰመራ በዓል ለ12ኛ ጊዜ የሚደረግ ነው። ከአፋር የመጀመሪያው የሰው ዘር መገኛ የሆነች ምድር፤ የሉሲ (ድንቅነሽ)፣ የሰላም የኢዳልቱ ካዳሙ እና የአርዲ ቅሬተ አካል የተገኘው ጥንተ ታሪካዊ አገር ነው።

አፋር ከሰው ዘር መገኛነቱ ባሻገር ድንቅና ማራኪ የተፈጥሮ ገፅታ፤ ውብ መልክዓ ምድር መሆኑን ለማረጋገጥ በኤርታ አሊ እና ዳሉል እሳተ ገሞራ የተፈጥሮ የህብረ ቀለማት ውህደትና በሚንተከተከው የእሳተ ጎሞራ ፍንጥቅጣቂ ዙሪያ ያለውን ድባብ ማየት ብቻ ይበቃል። ጨው የሚታፈስበትና የጨው አለት እየተደረመሰና እየተጠረብ በአሞሌነት የሚመረትበት አካባቢና የአፍዴራ ኃይቅ እንዲሁም የግመሎች ቅጥልጥልነት ቅፍለተ (Caravan) ያለውን ገፅታና ልዩ ትርኢት ማራኪነት በርካታ ቱሪስቶች የሚጎበኙት ቅዱስ ክልል ነው።

የአፋር ብሔራዊ ክልል በአገራችን ሰሜናዊ ምሥራቅ የሚገኝ አካባቢ ሲሆን፣ በሰሜን ምዕራብ በትግራይ ክልል፣ በደቡብ ምዕራብ በአማራ ክልል፣ በደቡብ ከኦሮሚያ ክልል፣ በሰሜን ምሥራቅ ከኤርትራ መንግሥት እና በምሥራቅ ከጅቡቲ ሪፐብሊክ መንግሥት ጋር ይዋሰናል። የአፋር ህዝብ ቋንቋ አፋርኛ ሲሆን ከኩሽ የቋንቋ ቤተሰብ ይመደባል። ህዝቡ በአብዛኛው አርብቶአደር ሲሆን፣ የተወሰኑ በከፊል አርብቶ አደርና በማዕድን ጨው ማምረት ዘርፍ የተሰማሩ አሉ። የአፋር ህዝብ ሙሉ በሙሉ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ሲሆን የሌላውን ሃይማኖትና እምነት የሚያከብር፤ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ጋር በመተባበርና በመቻቻል ለረጅም ዘመናት አብሮ የኖረ ህዝብ ነው። ለአገራችን ሰንደቅ ዓላማ ጽኑ ልባዊ ፍቅር ያለው ህዝብ ነው። የኢትዮጵያን ባንዲራ እንኳንስ የአፋር ህዝብ ቀርቶ የአፋር ግመሎችም ያውቃሉ።

የአፋር ክልልና ህዝብ የረጅም ዘመናት ታሪክ ባለቤት፣ የሰው ዘር መገኛ በመሆኑ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድትታወቅ አድርጓታል። በዚህ ረገድም በዩኔስኮ ከተመዘገቡት ስምንት የአገራችን ቅርሶች መካከል ዋናው የአፋር ክልል የታችኛው አዋሽ ሸለቆ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመት ያስቆጠረችው ሉሲን (ድንቅነሽ) ጨምሮ ሰላም፣ ኢዳልቱ፣ ካዳሙ እንዲሁም 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዓመታትን ያስቆጠረውና በቅርቡ የተገኘው አርዲ ቅሬተ አካል የአገራችንን የስልጣኔ ምንጭነት በዓለም ዙሪያ ከሚያስተጋቡ የሰው ዘር ቅሪተ አካላት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።

የአፋር ሕዝብ ታሪክ እንደሚያስረዳው ክልሉ ከኢትዮጵያ በድንበር አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ ከውጭ ለሚመጡ ጥቃቶችና ወረራዎች ባለመንበርከክ መክቶ በመከላከል የኢትዮጵያ አጥር በመሆኑ ለሀገሩ አንድነትና ነፃነት ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለ ህዝብ መሆኑ ይታወቃል። የአፋር ህዝብ በህብረት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ባህላዊ አስተዳደርና ማህበራዊ መስተጋብር ያለው ሲሆን በኢትዮጵያዊነቱ ፀንቶ የኖረ ለሀገሩና ለሰንደቅ ዓላማው የቆመ ህዝብ ነው። እንደማንኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የአፋር ህዝብ ለብዙ ዘመናት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን ተነጥቆ በፀረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ተረግጦ ሲማቅቅ የኖረ ህዝብ መሆኑ ይታወቃል። በጊዜው የነበረውን የጭቆና እና የአፈና አገዛዝ ለመገርሰስ ከሌላው ህዝብ ጋር በመታገል ዛሬ ላገኘነው ሕገመንግሥትና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት መስፈን የላቀ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

አፋር እንደ አዋሽ ያሉ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች እና በክረምት ጊዜ የሚሞሉ ውሃዎች የሚገኙበት ሰፊ የሆነው የአፍዴራ ኃይቅና ሌሎች የውሃ ቋቶች የሚገኙበት በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገ፤ ሰፊ የሆነው የአፍዴራ ኃይቅና ሌሎች የውሃ ቋቶች የሚገኙበት በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገ ሜዳማ፤ ለእርሻ አመቺ የሆነ መሬት ያለው በዳሉል አና በኤርታአሌ አካባቢ ካለው ድንቅ የተፈጥሮ ገጽታ ጋር የፍል ውሃና የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በመኖሩ በቱሪስት መዳረሻነት ተመራጭ አካባቢ ነው።

ክልሉ በ5 ዞኖች እና አርጐባ ልዩ ወረዳን ጨምሮ በ32 ልዩ ወረዳዎችና በ370 ቀበሌዎች የተዋቀረ ነው። የክልሉ ዋና ከተማ ሰመራ ሲሆን፣ ሌሎች ከተሞችም በተለይም በሎጊያ፣ አሳኢይታ፣ ዱብቲ፣ ሚሌ፣ አዳይቱ፣ ገዳማይቱ፣ አዋሽ አርባ፣ አዋሽ ሰባት እና ሌሎች ከተሞች ዛሬ በተሻለ ዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው። አሁን ደግሞ ከ12ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ጋር ተያይዞ በበዓሉ ምክንያት ከተገነቡት የመሰረተ ልማት ሥራዎች የክልሉን አቅምና ገጽታ በመለወጥ ረገድ ያላቸው አስተዋጽኦ ከተሞቹን የበለጠ ያጠናክራቸዋል። በተለይ ደግሞ በሰመራና ሎጊያ ከተሞች ያለው የልማት እንቅስቃሴ ከተማዎቹን ይበልጥ ዘመናዊ ያደርጋቸዋል ።

በሰመራ የተገነባው የአውሮፕላን ማረፊያ የሚገኝበት ደረጃ ከአዲስ አበባው ቦሌ ቀጥሎ ትልቁ ሲሆን ዘመናዊ ስታዲየም እና ልዩ ልዩ ሆቴሎች በዘመናዊ መልክ መገንባታቸው ወደ ክልሉ ለሚመጡ ቱሪስቶችና የአገር ውስጥ እንግዶች የተመቻቸ ሁኔታ ተፈጥሯል። ወደ አፋር የሚሄድ ሰው በቆይታው ሁለት ዓይነት የመኝታ አገልግሎት ያገኛል። መኝታ ክፍል መከራየት ወይም ውጭ በተዘረጋ የጠፍር (የሽቦ) አልጋ በአጐበር ጥላ ስር ማደር ይችላል። አሁን አየሩ ቀዝቀዝ ያለና ደህና የሚባል ነው። ከሰኔ እስከ ነሐሴ መጨረሻ ግን ሞቃታማ የአየር ጊዜ ቢሆንም አፋር ዓመቱን ሙሉ የተመቸ አካባቢ መሆኑ ተመራጭ እየሆነ ይገኛል።

በአፋር ሰመራ የሚከበረው 12ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሌሎች ክፍሎች እንደተከበሩት በዓላት ሁሉ በህዝቦች መከባበርና መቻቻል የሚጠናከርባት፤ በአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለህዳሴያችን ስኬት የበኩሉን አሻራ ጥሎ የሚያልፍ፤ በሰላም ተጀምሮ በሰላም የሚጠናቀቅ እንደሚሆን እናምናለን። ከሰመራው 12ኛ በዓል በቀጣይም በመጪዎቹ ዓመታት ይህ በዓል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እምነታችን ጽኑ ነው። የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ማለት ሕገ መንግሥት የፀደቀበት ቀን በመሆኑ በዓሉ ከመከበር የሚቋረጥበት ምክንያት መኖር የለበትም። የበዓሉ መከበር ይቁም ወይም ይቀጥል የሚል ጥርጣሬ አያስፈልግም። መቀጠል አለበት። የሕገ መንግሥታችንን ፋይዳ ወደ ውስጣችን ለማስገባት የፌዴራሊዝም ሥርዓታችንን አጠናክረን ለመቀጠል፤ የሕዝቦችን የእርስ በርስ መተዋወቅና ትስስር ለማስቀጠል፤ በዓሉ የማይተካ የራሱ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን እናምናለን። ምናልባት በበዓሉ ምክንያት በየዓመቱ የሚወጣው ወጪ መብዛት« ቢቀርስየሚል ጥያቄ ይቀሰቅስ ይሆናል። ይህ ግን ሰበብ እንጂ ምክንያት ሊሆን አይችልም። መፍትሔውም በዓሉን ማስቀረት ሳይሆን የፕሮግራሙን በጀት መቀነስና በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ነው። ከልክ በላይ የሆኑ ለታይታ ብቻ ለአንድ ጊዜ የወሬ ፍጆታ የሚውሉ የግንባታ ሥራዎችን ፈር ማስያዝ ሊያስፈልግ ይችላል። አውሮፕላን ማረፊያ ሊያስፈልግ ይችላል። ለቱሪስት ለእንግዶች ማረፊያ የሚሆኑ ሆቴሎችን መገንባት ሊያስፈልግ ይችላል። ስታዲየም መገንባትም ሊያስፈልግ ይችላል። ይሁን እንጂ ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግዙፍ ሆቴልና ግዙፍ ስታዲየም « ይሁን አይሁን» በሚለው ላይ ረጋ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ለወደፊቱ ትውልድ እያሰብን አሁን ያለውን ትውልድ ሃብት እንዳናባክን ወይም ለአሁኑ ትውልድ በቻ እያሰብን የወደፊቱን ትውልድ ራዕይ እንዳናጨልም፤ ከግብር ከፋዩ ሕዝብ የተገኘውን ገቢ በተገቢው መጠን አደላድሎ መጠቀም ከአመራሩ ይጠበቃል።

12ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የሚከበርባት አፋር በርካታ አስደሳች ወግ፣ ባህልና ማህበራዊ መስተጋብር ያለባት ታሪካዊ ምድር ናት። ለማጠቃለል ያህል ባለፉት ዓመታት የተከበሩት በዓላት የትና መቼ እንደተከበሩ እናስታውሳችሁ።

አንደኛውና የመጀመሪያው በዓል የተከበረው በ1999 .ም በአዲስ አበባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ባህል ማዕከል

ሁለተኛው በ2000 .ም ደቡብ ብሄር በሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል አስተናጋጅነት ሀዋሳ ከተማ

ሦስተኛው በ2001 .ም በኦሮሚያ ክልል አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ

አራተኛው በ2002 .ም በአምስቱ አጐራባች ክልሎች (አፋር፣ድሬዳዋ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ ሐረሪ) አዘጋጅነት በድሬዳዋ

አምስተኛው በ2003 .ም በአዲስ አበባ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ከተማ

ስድስተኛው በ2004 .ም ትግራይ-መቀሌ

ሰባተኛው- 2005 .ም አማራ- ባህርዳር

ስምንተኛው በ2006 .ም ሶማሌ- ጅግጅጋ

ዘጠነኛው በ2007 .ም ቤኒሻንጉል ጉሙዝ -አሶሳ

አሥረኛው በ2008 .ም ጋምቤላ

አሥራ አንደኛው በ2009 .ም ሐረር

መልካም ቀን ይሁንልን!

 

 

ግርማ ለማ

 

 

 

Published in አጀንዳ

 

በአገራችን ባለፉት 15 ዓመታት ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን ማስመዝገብ ተችሏል። ይህ ለውጥ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረገ ነው። ይህን ፈጣን ዕድገት ለማስቀጠልና የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ለማጎልበት እንዲቻል ሁሉም በየደረጃው ራሱን የሚያይበት መድረኮችን ተፈጥረው ሁሉም ራሱን የሚያይበት ዕድል ተፈጥሯል። ልማቱ ወደኋላ ሊጎትቱ የሚችሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍና በአገራችን የተጀመረውን የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለማጎልበት የሚያስችል ጥልቅ ተሃድሶ በየደረጃው ባሉት የተለያዩ አካላት ተካሂዷል።

ባለፈው ዓመት ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ፣ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮቹ፣ አባሎቹና ደጋፊዎቹ ጥልቅ ተሃድሶ አድርገዋል። ባለፉት 15 ዓመታት ፓርቲው እንደ መንግሥትና ድርጅት የተገበራቸው አሰራሮች፣ የተገኙ ውጤቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች በዝርዝርና በጥልቀት ታይተዋል። የአመራሮች ጥንካሬና ድክመት በስፋት ተፈትሸዋል። የመንግሥት ሠራተኛውም የጥልቅ ተሃድሶ መድረኮችን ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ባለው አደረጃጀት አካሂዶ ያለበትን ክፍተት ለይቷል። በተመሳሳይ ህብረተሰቡም የተሃድሶ መድረኮችን አካሂዷል። ይህ ለአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት፣ ለመልካም አስተዳደር መስፈን የሚኖረው ሚና ጉልህ መሆኑ አይካድም።በየደረጃው በተካሄዱ የጥልቅ ተሃድሶ መድረኮች ለስልጣን ያለ የተዛባ አተያይ የወለደው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ዋና ችግር መሆኑ ተለይቷል።የትግሉ ማእከል ይኸው ችግር ለመፍታት መሆኑንም አቅጣጫ ተቀምጧል።

የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ የሚሸነፈው ልማታዊ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ በመፍጠር እንደሆነ ይታመናል። የኪራይ ሰብሳቢነትን ለማስወገድ የሚደረገው ትግልም ዓመታትን የሚጠይቅ መሆኑን አይካድም። በአሁኑ ወቅት መወሰድ በጀመሩት እርምጃዎች በገጠር እና በከተሞች መሻሻሎች እየታዩ ነው። ይሁን እንጂ አሁንም ልማታዊ ፖለቲካ-ኢኮኖሚ በተለይ በከተሞች የበላይነት ያገኘበት ሁኔታ በሚፈለገው ደረጃ አልተፈጠረም። የተተኪው አመራር ፀረ የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ-ኢኮኖሚ ትግል ፈታኝ ያደርገዋል። ስለዚህ የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ -ኢኮኖሚ የበላይነት ባገኘበት ሁኔታ ኃላፊነቱን የሚወጣው አዲሱ አመራር ምን ያህል ከባድ ኃላፊነት የተሸከመ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

የጥልቅ ተሃድሶውን ተከትሎ ከአለፈው ዓመት ጀምሮ አመራሩን ለማስተካከል በተወሰዱት እርምጃዎች እና በጥልቅ ተሃድሶ ሕዝባዊ መድረኮች የተወሰኑ ችግሮች መፈታት ጀምረዋል።በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ከማንነት እንዲሁም ከወሰን ማካለል ጋር ተያይዘው የግጭት መንስኤ የነበሩት መፍትሄ እያገኙ ነው። አሁንም ግን ከፍተኛ የህዝብን እርካታ ማረጋገጥ በሚቻልበት ደረጃ ላይ አልተደረሰም፡፡ ስለዚህ የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄው በላቀ ህዝባዊ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች ለመፍታት አመራሩ የተተነተነ ምላሽ የመስጠት ብቃቱም አብሮ ማደግ ይገባዋል። ሙስናን፣ አድሏዊ አሰራርን፣ ያልተገባ ጥቅም ፈላጊነትን፣ የጥቅም ሰንሰለትን በየጊዜው እየበጣጠሱ መጓዝን ይጠበቃል፡፡ በድርጅቱም ሆነ በመንግሥት የሥራ ኃላፊነቶች ውስጥ ያሉ ተግዳሮቶችን በአግባቡ ተንትኖ በመረዳት ችግሩን ዘላቂነት ባለው መንገድ ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይገባል።

መንግሥት የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉን እያካሄደ ነው፡፡ ስለዚህ፤ መንግሥት ራሱን ከችግር አጽድቶ የህዝቡን እንባ ለማበስ ቁርጠኛ ቢሆንም፤ በተጨባጭ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አርኪ መሆን አልቻለም፡፡ የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል መጀመር ያስደነገጣቸው ቡድኖች እና የሥርዓቱ ባላንጣዎች የህዝቡን አጀንዳ ነጥቀው የጥያቄውን ውል እያጠፉት ይገኛሉ። የህዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከሰላማዊ የተቃውሞ ሂደት ወጥቶ የፀጥታ ሥጋት እንዲሆን እንቅልፍ አጥተው እየተረባረቡ ናቸው፡፡

መንግሥት መስተካከል የሚገባውን ነገር ለማስተካከል ጥረት እያደረገ ከህዝብ ጋር መምከር ሲጀምር፤ የተለያዩ ኃይሎች አጀንዳውን ሰርቀው በየአቅጣጫው እየጎተቱ፤ ችግሩን ከፌዴራል ሥርዓቱ ጋር በማያያዝ እና ብሔረሰባዊ ቅርጽ በማላበስ የፌዴራል አወቃቀሩን ማውገዝ ይዘዋል፡፡ ይህ ደግሞ ተገቢነት የሌለው በመሆኑ የተጀመሩት ጥረቶች የህዝቡን ጥቅም ከማስከበር አንፃር መቃኘት ስላለባቸው ህዝባዊ ውይይቶች ተጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል።

በሌላ በኩል፤ በህዝብ ብሶት ግሎ የተጀመረው የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል እንደ ደራሽ ጎርፍ ጠራርጎ ሊወስዳቸው መሆኑን የተረዱት ኪራይ ሰብሳቢዎች ፤ በየጊዜው የሚከሰተው ሁከት ከመጣባቸው አደጋ የማምለጥ ዕድል እንደሚሰጣቸው በማሰብ ጉዳዩን በማቀጣጠል ተሳታፊ እየሆኑ ይታያሉ፡፡ ይህን አካሄድ መንግሥት በሚገባ ተረድቶታል። በመሆኑም ከእያንዳንዱ ችግሮች በስተጀርባ ሆነው ችግሮቹን የሚያባብሱና የሚያቀጣጥሉ ወገኖችን አደብ እንዲገዙ ሊያደርጋቸው ይገባል።

ከጥልቅ ተሃድሶ እርምጃዎች በዘለለ የመንግሥት መዋቅራዊ አሰራርም ሊጠና ይገባዋል። የመንግሥት መዋቅርን ተጠቅሞ ያለአግባብ በስልጣኑ የሚጠቀም ፈጻሚ ተበራክቷል። የችግሮቹ ምክንያት ሲቃኝ የተጠያቂነት ስርዓት አለመጠናከሩን ያሳያል። መንግሥት በጥልቅ ተሃድሶ ግምገማው ባገኛቸው የመልካም አስተዳደር ጥሰቶችና ስልጣንን ካለ አግባብ በመጠቀም ላይ በነበሩ አመራሮችና ፈፃሚዎች ላይ እርምጃ መውሰዱ እሰየው የሚያስብል መሆኑ አይካድም። ግን ሰዎችን በማሰር ብቻ የሚቋጭ መሆን የለበትም። ሰዎችን የሚያስራቸውና ከስልጣናቸው የሚያስወግዳቸው ቋሚ የአሰራር ሥርዓት ሲኖር ነው። በመሆኑም አስፈጻሚው አካል ተጠያቂ መሆኑን የሚያጠናክር ተቋማዊ አሰራር ማጠናከር ያስፈልጋል። በመሆኑም መንግሥት በአጥፊዎች ላይ መውሰድ የጀመረውን እርምጃ ተቋማዊና ቀጣይነት ባለው መልኩ ማከናወን ይኖርበታል።

 

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ

 

በአገሪቱ ያሉ አምስት የምጥን ማዳበሪያ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅም እዲያመርቱና አሠራራቸውን እንዲያሻሽሉ ይረዳ ዘንድ የአስተዳደር ሥራውን ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ‹‹ኦሲፒ›› ለተሰኘው የሞሮኮ ኩባንያ እንደሚሰጥ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ በግብርና ግብዓት የኢ-ኩፖን ሽያጭ ሥርዓትን ለመተግበር እና ለማስፋፋት በዚህ ዓመት 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር መመደቡ ተገልጿል፡፡

ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በቾ ወሊሶ፣ መርከብ፣ መልህቅ፣ እንደርታ እና ጊቤ ደዴሳ የተባሉት አምስቱ ነባር ምጥን ማዳበሪያ አምራች የሕብረት ሥራ ዩኒዮኖች የአስተዳደር ሥራ ለማከናወን በድሬዳዋ ግዙፍ ማዳበሪያ ፋብሪካ እየገነባ ለሚገኘው ‹‹ኦሲፒ›› ለተባለው የሞሮኮ ኩባንያ ለማስረከብ ሂደቶች ተጀምረዋል፡፡

መረጃው እንደሚያስረዳው አስተዳደራዊ ሥራው ለ‹‹ኦሲፒ›› ኩባንያ እንዲሰጥ የተወሰነው ፋብሪካዎቹ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ባለመሆናቸውና በውስብስብ ችግሮች ውስጥ በመቆየታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ በመታቀዱ ነው፡፡

ድርጅቱ የአምስቱን ነባር የምጥን ማዳበሪያ ፋብሪካዎች የአስተዳደር ሥራ የሚያከናውነው ያለ አንዳች ጥቅም ትስስር ሲሆን፤ ዩኒዮኖቹ አቅም ሲፈጥሩ አስረክቦ የሚወጣ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ዩኒዮኖቹም ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ተገልጿል፡፡

በተያያዘ ዜና በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ ግብዓት ግዥ እንዲፈጽም ዘመናዊ አሠራር እየተዘረጋ ነው፡፡ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የሩላር ፋይናንስ ዳይሬክተር አቶ ኃይለመለኮት ተክለጊዮርጊስ እንደገለጹት፤ አርሶአደሮች ከወረቀት ንክኪ ነፃ በሆነ አሠራር ኤሌክትሮኒክስ ኩፖን በመጠቀም የግብዓት ግዥ መፈፀም ያስችላቸዋል፡፡ አርሶአደሮች ግብዓት ለመግዛት ሲፈልጉ የሚመለከተው አካል ዘንድ በመሄድ ብር ይከፍላሉ፡፡ በመቀጠልም ኩፖን በመያዝ ግብዓት እንዲገዙ ይደረጋል፡፡

በዚህ አሠራር አርሶአደሮች በማናቸውም ሰዓት የግብዓት ግዥ መፈፀም እንደሚያስችላቸው የጠቆሙት አቶ ኃይለመለኮት፤ ይህ አሠራር በአሁኑ ወቅት በሙከራ ደረጃ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

 

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

 

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።