Items filtered by date: Tuesday, 05 December 2017

ከዓመታት የማጣሪያ ውድድሮች በኋላ በሩሲያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው በስፖርት አፍቃሪው ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው የ2018 የዓለማችን ታላቁ የእግር ኳስ መድረክ ሊጀመር የወራት ዕድሜ ቀርቶታል። ከወዲሁም ያልተጠበቁ ክስተቶችን ማመልከት ጀምሯል። በፍልሚያው ሜዳ የተጠበቁት ሲቀሩ፤ ያልተጠበቁት የተሳትፎ ትኬት ቆርጠዋል። የመድረኩ ድምቀቶች ብርቱካናማዎቹ ሆላንዶች እና ጣሊያኖች በአይስላንድ እና በፓናማ ተተክተዋል።

በመድረኩ በአምስት አገራት የምትወከለው አህጉራችን አፍሪካም ብትሆን አብዛኞቹን ተወካዮቿን ቀይራለች። ከአራት ዓመት በፊት በነበረው መድረክ በጋና፤ ካሜሮን፤ ኮትዲቯር፤ ናይጄሪያና አልጄሪያ የተወከለችው አፍሪካ፤ ከአራት ዓመት በኋላ ናይጄሪያዎችን አስቀርታ አራቱን ቀይራለች። የተሳታፊዎቹን 32 አገራት አስቀድሞ ያስተዋወቀን የዓለም ዋንጫም ከቀናት በፊት ተሳታፊ ብሄራዊ ቡድኖቹን በምድብ ከፋፍሎ የመጀመሪያ ዙር ተፋላሚዎቻቸውን ይፋ አድርጓል።

በምድብ አንድ

በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ 65ኛ ደረጃ ላይ ለሚገኙትና የዓለም ዋንጫው አስተናጋጆች ለሆኑት ሩሲያዎች ከምድባቸው በጊዜ መሰናበት ከምንም በላይ የማይዋጥ ነው። እናም አንድ ጨዋታ መሸነፍ የሚያስከፍለውን ዋጋ ጥንቅቀው ያውቁታል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበሩበትን የፖለቲካ አቅምና አቋም በስፖርቱም መስክ ማሳየት ይፈልጋሉ። ለዚህ ዓላማቸው ተፈፃሚነትም ልምድ ያላቸውን አላን ድዛጎኤቭ፤ ፊዮዶር ስሞሎቭ የመሳሰሉ ኮከቦች ላይ ተስፋ ጥለዋል። ለውድድሩ ዝግጅት የሰጡትን ትኩረት በእግር ኳሱ ፍልሚያ መድገም ከቻሉም ታሪክ ይፅፋሉ።

ከጣሊያኑ 1990 የዓለም ዋንጫ ወዲህ ዓመታትን ቆዝመው ዳግም ወደ ታላቁ መድረክ የተመለሱት የአፍሪካ ተወካዮቹ ግብፆችም ቢሆኑ በሩሲያው መድረክ ያልተጠበቀ አስደማሚ ታሪክ መፃፍ ይፈልጋሉ። «ግብፃዊው ሜሲ» የሚል ቅፅል ከተሰጠው ውድ ልጃቸው መሃመድ ሳላህና ከአርሴናሉ ኮከብ መሃመድ አልኒኒ ብዙ ተዓምር ይጠብቃሉ።

በሉዊስ ሱዋሬዝ ልዩ ክስተቶች የምትታጀበው ኡራጓይ ከባርሴሎናው ኮከብ በተጓዳኝ በፓሪሴን ጄርሜኑ የጎል አውራ ኤዲሰን ካቫኒ ላይ ዕምነት ጥላለች። ከ1950 ወዲህ ዋንጫ ማንሳት ያልሆነላቸው ኡራጎዮች በሩሲያ ምድር የዋንጫ ረሃባቸውን ለማስታገስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም።

እግር ኳስ ሲነሳ እምብዛም ስሟ አብሮ የማይነሳውና በቀድሞው የአርጀንቲና አሰልጣኝ ኤድጋርዶ ባውዛ የምትመራው የመካከለኛው ምስራቅ አገር ሳዑዲ ዓረቢያ በሞስኮ ሰማይ ስር ያላትን አቅም ለማሳያት ዝግጅቷን አጠናቃለች። ከዚህ ምድብ ኡራጋይና ግብፅ በኮከብ ተጫዋቾቻቸው ብቃት ታግዝው ወደ ቀጣዩ ዙር እንደሚያልፉ ተገምቷል። ክብር የሚሰጠው የመክፍቻ ጨዋታ በሳዑዲና ሩሲያ መካከል ይደረጋል።

ምድብ ሁለት

2016 የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊዋ ፖርቹጋል የአውሮፓ ኃያልነቷን በዓለም አቀፍ ደረጃ መድገም አቅዳለች። ይህን ኃላፊነትም ለዓለማችን ኮከብ የግብ ማሽን ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአደራ ሰጥታለች። ተጫዋቹ ከሰሞኑ እያሳየ በሚገኘው ደካማ አቋም ከቀጠለ ግን የአውሮፓ ሻምፒዮኖቹ የሚፈለጉት ሳይሆን የማይፈልጉት መሆኑ አይቀሬ ነው።

ስፔኖች ከስምንት ዓመታት በፊት በደቡብ አፍሪካ የፃፉትን ወርቃማ ታሪክ በሩሲያ ምድር ዳግም ማድመቅ ይፈልጋሉ። በወጣት ተጫዋቾቿ ተወክላ ወደ ሞስኮ የምታቀናው ስፔን፤ ከፍተኛ የማሸነፍ ግምት ካላቸው አገራት አንዷ ብትሆንም የቀድሞው አስፈሪነቷ ግን አሁን ያለ አይመስልም።

1978 በዓለም ዋንጫው መድረክ ጨዋታን በማሸነፍ ከአፍሪካ ቀዳሚ የመሆን ከብር ያገኙት የሰሜን አፍሪካዎቹ ድንቅ ልጆች ሞሮኮዎች፤ የዓለም ዋንጫው ልዩ ክስተት እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ሞሮኮዎች በመጨረሻው የምድብ የማጣሪያ ጨዋታ በጠንካራ ስብስብ የተዋቀረው የኮትዲቭዋር ቡድን አሸንፋው ሩሲያ የሚወስደውን ትኬት መቆረጣቸው ይታወሳል። የዚህ ምድብ ሌላኛዋ አገር ኢራን ናት። ወደ ዓለም ዋንጫ ስታልፍ የአሁኑ አምስተኛዋ የሆነው ኢራን ከዚህ ቀደሙ የተሻለ አዲስ ውጤት ታስመዝግባለች ተብሎ አይጠበቅም። የታላቁን መድረክ የመጀመሪያ ፈተና ማለፍ ስለመቻሏም ከራሳቸው በቀር ማንም አይተማመንም።

ከዚህ ምድብ ፖርቱጋልና ስፔን በቀላሉ ወደ ቀጣዩ ዙር ያልፋሉ ተብሎ የተገመተ ሲሆን የሁለቱ አገራት ጨዋታም የመድረኩ ትልቅ ጨዋታ እንደሚሆን ታምኖበታል። በሁለቱ አገራት ጨዋታ ክርስቲያኖ ሮናልዶም ከግማሽ በላይ ከሚሆኑ የሪያል ማድሪድ ቤት ጓደኞቹ ጋር ለተቃራኒ ዓላማ ይፋጠጣል። ስፔናዊው የሪያል ማድሪድ ተከላካይ ሰርጂዎ ራሞስም ሮናልዶን ለማቆም አለኝ የሚለውን ብቃት አሟጦ ይጠቀማል።

ምድብ ሦስት

1998 የዓለም ዋንጫ አዘጋጅና የዋንጫው ባለቤት ፈረንሳይ ባለተሰጥኦ የወጣት ተጫዋቾችን የያዘ ስብስብ ይዛ ሞስኮ ትደርሳለች። በሰላማዊው የፍልሚያ መድረክ ለማንቸስተር ዩናይትዱ ፖል ፖግባ፣ ለቼልሲው የመሃል ሜዳ ሞተር ንጎሎ ካንቴ የመሃል ደጀን ኃላፊነቱን ስትሰጥ፤ የአትሌቲኮ ማድሪዱ አንቷን ግሪዝማን ደግሞ የግብ ኃላፊነቱን ይረከበዋል።

አሰልጣኝ ዲዲየር ዴሻም ብቁ ተፎካካሪና አሸናፊ ለመሆን የተጫዋቾችን የግል ብቃት ወደ ቡድን የማምጣት ከባድ ኃላፊነት ተጥሎበታል። የዘንድሮ የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ዋንጫ ካላነሳም መቼም አያነሳም የሚል አስተያየት ከወዲሁ መሰጠት ጀምሯል።

እ ኤ.አ ከ2010 በኋላ በዓለም ዋንጫው ስትሳተፍ የመጀመሪያዋ የሆነችው ዴንማርክ ቀጣዩ የዓለም ዋንጫ አምስተኛ ተሳትፎዋ ነው። ዴንማርኮች በብራዚል ከውድድሩ በወጡበት የ1998ቱ የዓለም ዋንጫ እስከ ሩብ ፍፃሜ መጓዝ መቻላቸው ይታወሳል፡፡ ዘንድሮ ከዚህ የተሻለ ታሪክ ለመሥራት ለቶተንሃሙ አማካይ ክርስቲያን ኤሪክሰንን ከባድ ኃላፊነት አስረክባለች።

የዘንድሮው የአውስትራሊያ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ በተከታታይ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን በአጠቃላይ ግን አምስተኛዋ ነው። ጥሩ ተሳትፎ አድርጋበታለች የሚባለው በ2006 በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ላይ ሲሆን፤ ከመጨረሻዎቹ 16 ቡድኖች ገብታ ከጣሊያን ጋር ባደረገችው ጨዋታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃ በተሰጠባት ፍፁም ቅጣት ምት ተሸንፋ የወጣችበት ነው።

የደቡብ አሜሪካዋ ፔሩ በሞስኮው ፍልሚያ የሎኮሞቲቭ ሞስኮውን ጨዋታ ቀያሪ ጀፈርስን ፋርፋንን ተስፋ አድርጋለች። በዚህ ምድብ የዓለማችንን ውድ ተጫዋች ይዛ መድረኩን የምትቀላቀለው ፈረንሳይ በኮከቦቿ ተዓምር ከምድቧ ማለፏ ጥርጥር አይኖረም። ዴንማርኮችም ለሁለተኛነት ሰፊ ግምት አግኝተዋል።

ምድብ አራት

በዚህ ምድብ የአህጉራችን ተወካይ ናይጄሪያ የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮን መሆን ከቻሉት በኮከቦች ስብስብ ከተዋቀሩት አርጀንቲናዎች ትፋጠጣለች። ከ1994 የአሜሪካ የዓለም ዋንጫ ወዲህ አንድ የዓለም ዋንጫ ብቻ ያመለጣቸው ንስሮቹ፣ በማጣሪያ ጨዋታዎች የነበራቸው ያለመሸነፍ ጉዞ በሩሲያው ታላቅ እግር ኳስ መድረክ ይደግሙታል ተብለው እንዲጠበቁ አድርጓቸዋል።

ቪክቶር ሞሰስ፣ የአርሴናሉ አሌክስ ኢዮቢ እና ሌሎችም ተጫዋቾች ያካተቱት ንስሮቹ፤ በተለይም በምድብ ማጣሪያዎች በየጨዋታው በአማካይ ሁለት ግብ እያስቆጠሩ መምጣታቸው የማጥቃት አጨዋወታቸው ማሳያ ተደርጓል።

አርጀንቲና አንሄል ዲማሪያ፣ ሰርጂዮ አጉዌሮ፣ ሊዮኔል ሜሲ፤ ኩን አጉዌሩ፤ ጎንዛሎ ሄጊዌን እንዲሁም የጁቬንቱሱን ጨዋታ ቀያሪ ፓውሎ ዲያባላን በመሳሰሉ ኮከቦች ብትወክልም ወደ መድረኩ ለመምጣት በእጅጉ ተቸግራ መታየቷ በሩሲያው መድረክ ብዙም ግምት እንዳይሰጣት አድርጓል። ይሁንና አስፈሪ ቡድን መያዟ እርግጥ ነውና የዋንጫ ግምት የሚሰጧትም በርካታ ሆነዋል።

ሉካ ሞድሪች፣ ኢቫን ራኪቲች፣ ማሪዮ ማንዙኪች፣ ኢቫን ፔርሲችና ኒኮላ ካሊኒችን የመሳሰሉ በድንቅ ክህሎት የታገዙ ብቁ ተጫዋቾች ባለቤት የሆነችው ክሮሺያ የመድረኩ ክስተት ትሆናለች ተብሎ ትጠበቃለች።

የሩሲያው የዓለም ዋንጫ ለአይስላንዶች የመጀመሪያ ተሳትፏቸው ነው። በኮከቦች ከተዋቀረችው አርጀንቲና ጋር የመጀመሪያ ጨዋታዋን የምታደርገው ትንሸ አገር ምንም እንኳን በሩሲያው መድረክ ብዙ ርቀት ትጓዛለች ተብሎ ባይገመትም መድረኩን መቀላቀሏ ብቻውን እንደ ስኬት ይቆጠርላታል።

ምድብ አምስት

የሩሲያው የዓለም ዋንጫ ከየትኛውም ብሄራዊ ቡድን በላይ ለብራዚሎች የላቀ ዋጋ አለው። የአምስት ጊዜ የዋንጫው ባለቤት ብራዚል፤ የቀደመ የእግር ኳስ ኃያልነት ተምሳሌትነቷን እና ከአራት ዓመት በፊት ራሷ ባዘጋጀችው መድረክ የደረሰባትን ሃፍረት ለመቀልበስ ሌላ ተጨማሪ ዓመት መጠበቅ አትፈልግም።

ኔይማር ጁኒየር፤ ጋብሬል ጀሱስ እና ፊሊፔ ኮቲንሆ የመሳሰሉ ምትሃተኛ ተጫዋቾችን የያዙት ቢጫ ለባሾቹ፤ በዓለም ዋንጫው እያንዳንዱ የማጣሪያ ጨዋታ ያሳዩትን አቅምና አቋም በዋናው ውድድር የሚደግሙት ከሆነ የፍላጎታቸውን እንደማያጡ ጥርጥር የለውም።

የማጣሪያ ጨዋታዎችን በብቃት አሸንፈው ወደ ዓለም ዋንጫ መግባታቸውን ካረጋገጡ አገራት አንዷ ስዊዘርላንድ ናት። አገሪቱ የውድድሩ ልዩ ክስተት ከሚሆኑ ክለቦች መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ስትሆን፣ ዤርዳን ሻኪሪ፣ ብሬል ኤምቦሎ፣ ግራኒት ዣካ፣ የተለየ አቋም ያሳያሉ ተብሎ ይጠበቃሉ።

ከዚህ ምድብ ኮስታሪካና ሰርቢያ ዝቅተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል። ብራዚልና ሲውዘርላንድ የታላቁን መድረክ የመጀመሪያ ፈተና በማለፍ ወደ ቀጣዩ ዙር እንደሚያልፉ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የሊቨርፑሉን ፊሊፕ ኩቲኒሆን ከአርሴናሉ ግራኒት ዣካ የሚያፋጥጠው የሁለቱ አገራት ጨዋታም ከወዲሁ ተጠባቂ ከሆኑት ትርታ ተመድቧል።

በምድብ ስድስት

ከአራት ዓመት በፊት በድንቅ ቡድናዊ ጥምረትና ሜሱት ኦዚልን በመሳሰሉ ድንቅ ተጫዋቾች ግላዊ ብቃት ዋንጫውን ማነሳት የቻሉት የወቅቱ የዓለማችን ቁጥር አንድ ብሄራዊ ቡድን የሆኑት ጀርመኖች፤ ያለፈውን ታሪክ ዘንድሮም መድገም ይፈልጋሉ። ቶማስ ሙለርና ቶኒ ክሩስን በመሳሰሉት ተጫዋቾች ጠንካራ ቡድን መመስረታቸውን ዋቢ በማድረግ ያለፈውን ድል እንደሚደግሙት የማይጠራጠሩት ከሚጠ ራጠሩት ይልቃሉ።

ሜክሲኮ ከዚህ ቀደም በነበሩት የዓለም ዋንጫዎች የነበራትን ምርጥ ተፎካካሪነት አሁንም እንድትጠበቅ ያደርጋታል። የውድድሩ ድምቀትና ክስተት እንደምትሆን የማትጠረጠር ሌላኛዋ አገር ስውዲን ናት። ለዘጠነኛ ተከታታይ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ጨዋታ መሳተፏን ያረጋገጠችው የእስያ ዞን ተወካይዋ ደቡብ ኮሪያ የቶተንሃሙን ኮከብ ሰን ሄዩንግ ሚን እና ሌሎችም ተጫዋቾች ይዛ ለተቃራኒ አገራት ፈታኝ እንደምትሆን ይጠበቃል። ጠንካራ ምድብ ከተባለው ከዚህ ምድብ ጀርመኖች በቀላሉ እንደሚያልፉ ጥርጥር የለውም። ከሲውዲንና ከሜክሲኮ ማን ያልፋል የሚለውን ግን መገመት አዳጋች ሆኗል።

ምድብ ሰባት

ይህ ምድብ ምርጥ ጨዋታ ይታይበታል ከሚባሉ ጨዋታዎች መካከል ተከታይ እንጂ ቀዳሚ የለውም። በጋሬዝ ሳውዝጌት የሚመሩት ሦስቱ አናብስት እንግሊዞች በማጣሪያ ጨዋታዎች ወደ ዓለም ዋንጫው ለመግባት ያሳዩት አቋም እጅግ ተደንቆላቸዋል። በቶተንሃሞቹ ጨዋታ ቀያሪዎች ሃሪ ኬንና ዴሌ አሊ ፊት አውራሪነት የሚመሩት አናብስቶቹ፣ ከ 1966 በኋላ የዓለም ዋንጫውን ዳግም ወደ ለንደን ይዘው መመለስ ከቻሉ ለቡድኑ አባላት በርከት ያለ ገንዘብ ተመድቦላቸዋል።

ወደ ሩሲያ ከሚያቀናው የቤልጄም ብሄራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ በእንግሊዝ ምድብ የሚጫወቱ 19 ጨዋታዎች አሉ። ዓለም በማግባትና ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል የመሰከረላቸው ኬቪን ደ ብሩይነ፣ ኤዲን ሃዛርድ እና ሮሜሉ ሉካኩ የመሳሰሉ ቁልፍ ተጫዋቾችን ይዛ ወደ ሞስኮ የምትገባው ቤልጄም፣ ለሦስቱ አናብስት ፈታኝ እንደምትሆን ጥርጥር የለውም።

ቱኒዚያ በዓለም ዋንጫ ስትሳተፍ የአሁኑ አምስተኛዋ ነው፤ የአሁኑ ብሄራዊ ቡድኗ ስብስብ በዋናነት ከአገር ውስጥ ክለቦች የተውጣጣ ነው። የአፍሪካዋ ተወካይ በጠንካራ ምድብ ውስጥ እንደ መገኘቷ በርካታ ወገኖች ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፏን እንዲጠራጠሩ ሆነዋል። ከዚህ ምድብ ዝቅተኛ ግምት ያገኘችው ፓናማ ሆናለች።

ምድብ ስምንት

በሩሲያ የዓለም ዋንጫ ልዩ ክስተት እንደሚሆኑ ከሚጠበቁ ብሄራዊ ቡድኖች መካከል ሴኔጋሎች ይካተታሉ። የምዕራብ አፍሪካዋ አገር በ2002 በእነ አል ሃጂ ዲዩፍ ፊት አውራሪነት እየታገዘች የሠራችው ገድል ሁሌም የሚታወስና ታሪክ ተሻጋሪ ነው። የሊቨርፑሉን ፈርጣማ ግብ አዳኝ ሳዲዮ ማኔ ድንቅ ብቃት በሩሲያ ከሚደምቁት አፍሪካዊ አገራት አንዷ የሆነችው ሴኔጋል፤ የዘንድሮ ስብስብም ጥንካራ እንደሆነ በበርካታ ወገኖች ተመስክሮለታል።

ሃሜስ ሮድሪጌዝ፣ ራዳሜል ፋልካኦ፣ ሁዋን ኳድራዶ፣ ዬሪ ሚና እና ዳቪንሰን ሳንቼዝን ይዛ ወደ ሞስኮ የምታቀናው የደቡብ አሜሪካዋ የኮከቦች መፍለቂያ ኮሎምፒያውም የሞስኮ ሌላ ድምቀት ናት። አውሮፓዊቷ ፖላንድም ብትሆን ቀላል ግምት የሚሰጣት አይደለችም። የባየር ሙኒኩ አስፈሪ አጥቂ ሮበርት ሌዋንዶውስኪ አገር በዓለም ዋንጫው ብዙ ርቀት መጓዝ እንደምትችል በርካታ ወገኖች ጥርጣሬ ውስጥ አልገቡም።

ሌላኛዋ የዚህ ምድብ ተካፋይ የሆነች አገር ጃፓን ናት። ምንም እንኳን በእግር ኳስ የሚሆነው ባይታወቅም፤ የኤሲያ ተወካይዋ በመድረኩ ታሳያለች የሚባለው ውጤት ዝቅተኛ ነው፡፡ የታላቁ መድረክ የመጀመሪያ ፈተና የማለፋቸው ነገር ያጠያይቃል። ቀላል ምድብ እንደሆነ በተለየው በዚህ ምድብ ኮሎምፒያ እና ሴኔጋል ወደ ቀጣዩ ዙር እንደሚያልፉ ከወዲሁ መገመት ጀምሯል።

 

ታምራት ተስፋዬ

Published in ስፖርት

ከዓለም እስከ አህጉር፣ ከአህጉር እስከ አገር፣ ከአገር እስከ ቀበሌ ብሎም ማህበረሰብ ከዚያም እስከ ግለሰብ፣ ከትልቅ እስከ ትንሽ በእግር ኳስ ልቡ ያልተሳበና ለስፖርት ፍቅር ያልተንበረከከ የለም ብሎ መናገር ይቻላል። ስፖርት ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት፣ ርዕዮተ ዓለምና የኢኮኖሚ አቅምን ሳይለይ የዓለም ህዝብን የሚያስተሳስርና የሚያገናኝ ድልድይ ነው። ተወዳጅ እንዲሆን ያደረገው ቀዳሚ ምክንያት ደግሞ ይኸው ነው።

ማንኛውም ስፖርት ያለምንም ደም መፋሰስና ያለምንም ውዝግብ በአገራት እንዲሁም በክለቦች መካከል ለአሸናፊነት የሚደረግ የፉክክር መድረክ ነው። ሰላማዊ ጦርነት የሚል ቅፅል ስም የሚሰጠውም ለዚሁ ነው። በየትኛውም ስፖርታዊ እንቅስቃሴና ክንዋኔ፤ ከአሸናፊነትም ጭምር ቀዳሚ የሚሆነው ደግሞ ስፖርታዊ ጨዋነት ነው። ስፖርታዊ ጨዋነት ከሌለ ስፖርት የለም፤ ያለስፖርታዊ ጨዋነት አሸናፊነትም አይኖርም።

በተለይ በርካታ የስፖርቱ አፍቃሪዎች «በማራኪነቱ፣ በልብ ሰቃይነቱ፣ በአስፈንዳቂነቱም ሆነ በአሳዛኝነቱ ወደር አይገኝለትም» ሲሉ በሚመሰክሩለት እግር ኳስ፣ ስፖርታዊ ጨዋነት፣ ከምንም በላይ ዋጋ ያለውና የሚያሸልም ነው።

እግር ኳስ በመዝናኛነቱ እንዲቀጥል ሰላማዊ የውድድር መድረክ መፈጠሩ የግድ ነው። ስኬታማ ሊግ ለመመልከት ደግሞ ጊዜና ገንዘቡን ወጪ አድርጎ፣ ፀሐይና ብርድ ሳይበግረው፣ ተስፋ አስቆራጩን ሰልፍ ተቋቁሞ ስታዲየም የሚገኘው የስፖርት ቤተሰብ የአደጋገፍ ሥርዓትና ስፖርታዊ ጨዋነት ወሳኝነት አለው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን በሚዘጋጁ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች በተለይ በእግር ኳሱ፤ በተጫዋቾች፣ በአሰልጣኞች፣ በዳኞች እንዲሁም በደጋፊዎች ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጭ የሆኑ ክስተቶች ሲደርሱ ተስተውሏል።

የአንዱ ክለብ ደጋፊ የተቃራኒ ክለብን፣ አንዱ ክልል ሌላኛውን ክልል፣ የተጫዋቾችን፣ አሰልጣኞችን እና የክለብ ባለቤቶችን ሳይቀር በስም ጠቅሶ ቃላት ከመወራወር አልፎ ግብግብ ገጥሞ ጨዋታን እስከ መረበሽ የደረሰ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት አይተናል።

በእርግጥ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ፌዴሬሽኑ፤ የፀጥታ ኃይሎች፣ ክለቦች፣ ደጋፊዎች እንዲሁም የደጋፊዎች ማህበራት የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደልን ለማስቀረት የተለያዩ ተግባራት ማከናወናቸው አይካድም፤ ይሁንና የእነዚህ ተግባሮች ዘር ፍሬ ያፈራ አይመስልም።

ሜዳ ገብቶ ጨዋታ የሚበጠብጥና በስታዲየሞች ላይ ጉዳት የሚያደርስ ተመልካች በሊጉ ጨዋታዎች ላይ መመልከት የተለመደ ሆኗል። ለዚህ ደግሞ ሩቅ ሳንሄድ ከተጀመረ የአምስት ሳምንታት ዕድሜን ያስቆጠረውን የዘንድሮውን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መቃኘት በቂያችን ይሆናል። ለምሳሌነት ደግሞ የወላይታ ዲቻና የሃዋሳ ከነማን ጨዋታ መጥቀስ እንችላለን።

እዚህ ላይ በዘንድሮው በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጨዋታ ላይ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት በተፈጠረው ግጭት እግር ኳሱን ለመታደም በተገኘው የስፖርት ቤተሰብ ላይ የደረሰው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት መረሳት አይኖርበትም።

እናም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እግር ኳስ መስከን የሚፈልግ ጉዳይ አለ። የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር በጣም እየተወራባቸው በሄደ ቁጥር በተቃራኒው እየባሰ የመጣ ይመስላል። በእግር ኳስ ሁነት ማሸነፍና መሸነፍ ያለና ወደፊትም የሚኖር ቢሆንም፣ የአሸናፊነት አስተሳሰብን ብቻ ይዞ ወደ ሜዳ መግባት ተጀምሯል። ጨዋታዎችን ለመታደም ወደ ካንቦሎጆ የሚያቀኑ ተመልካቾች በሥጋት ተወጥረዋል።

ዝምታችን ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡ የስታዲየም ድምቀትና ለእግር ኳሱ ውበት ዋና ተዋናይ የሆኑ ደጋፊዎች የድጋፍ ሥርዓት መልኩን ቀይሯል። ቀደም ባሉት ጊዜያት ከስታዲየሞቻችን የሚሰሙት ህብረ ዝማሪዎች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየደበዘዙ አፀያፊ ስድቦችና ፀብ አነሳሽ ድርጊቶች ጎልተው መሰማትና መታየት ጀምረዋል።

ተጫዋቾቻችንም ቢሆኑ ማንኛውንም ቅሬታ እና ተቃውሞ ቢኖራቸውም ስፖርታዊ ጨዋነትን በተመረኮዘ መልኩ ማቅረብ ትተዋል። ደጋፊዎችን በማያነሳሳና መጥፎ ስሜት ባልተንፀባረቀበት ሁኔታ ቅሬታቸውን ማቅረብ ጀምረዋል።

ደጋፊዎች ከእግር ኳሱ የፍልሚያው ሜዳ አጥር ክልል ገና ሳይዘልቁ በሜዳ ላይና በአደባባይ መደባደብ ጀምረዋል። ከፍተኛ የንብረት ውድመቶች የሰው ጉዳት አልፎም ህይወት እስከ መንጠቅ ደርሷል። ከካንቦሎጆው መንደር ከተቃራኒ ደጋፊ ጋር አብሮ መግባትም ሆነ እግር ኳሳዊ በሆነ ቋንቋ መግባባትና መወያየት የማይታሰብ እየሆነ መጥቷል። በተለይ በአንዳንድ የሊጉ ጨዋታዎች የስፖርታዊ ጨዋነት ስነ ምግባር በአደባባይ ክብርና ካባውን ይገፈፋል።

ይህን ተከትሎ የሚነሱ ግርግሮች ሥጋትም ስታዲየሞቻችን ለህፃናት፣ በዕድሜ ለገፉ ሰዎች፣ ሴቶችና ለአካል ጉዳተኞች ምቾት የሚነሱ እንዲሆኑ አድርገዋል። አዳዲስ ተመልካችን ለመመልከት እስኪያቅትም የካምቦሎጆው መንደር ለእንግዶቹ በሩን የዘጋ መስሏል።

ጨዋታዎች በታቀደላቸው የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ አቁመው፤ ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፍ ጀምረዋል። ከቀናት በፊት በተከሰተ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር የመቀሌና የወልዲያ ከተማ ጨዋታ እንዲራዘም መደረጉ ለዚህ ምስከር ይሆናል።

ይህ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር የአንድ እና የሁለት ክለቦች ደጋፊዎች ችግር ብቻ አይደለም። የአብዛኞቹ ወደ መሆን ተሸጋግሯል። አንድ እርምጃ ፈቀቅ ማለት በተሳነው እግር ኳሳችን መሰል ክስተቶች መመልከት በእጅጉ ያበሳጫል፣ ያሳፍራል።

ማንም በግልፅ እንደተመለከተው ባለፈው ዓመት የፕሪሚየር ሊጉ መገለጫዎች እስከሚመስሉ የተስተዋሉና የአገሪቱን እግር ኳስ መቀመቅ የሚከቱ ችግሮች በዘንድሮው የሊግ ጨዋታዎች ገና ከጅማሮ አይታዩ ናቸው።

ታዋቂው ሊቅ አልበርት አንስታይን እንደሚለው፤ አንድን ተመሳሳይ ነገር ደጋግሞ በመሥራት የተለየ ውጤት መጠበቅ አይቻልም። እኛም ተደጋጋሚ ተግባር እየፈፀምን የተለየ ውጤት መጠበቅ አይኖርብንም። እናም አካሄዳችንን ዳግም ማጤን የግድ ይለናል፡፡ ተግባሩን በሚፈፅሙት ላይ የሚወሰደው የቅጣት እርምጃ ክስተቱ ዳግም እንዳፈፀም የማስተማር አቅም ያለው ሊሆን ይገባል፡፡

የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ከተጀመረ አምስት ሳምንቶች ብቻ ቢቆጠሩም፤ በዚህ ጥቂት ሳምንት የተከሰቱ የስፖርታዊ ጨዋነት ግድፈቶች ሲመዘኑ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ እንደማያስፈልግ አመላካች መሆናቸውን መረዳት ይኖርብናል።

በዚህ ከቀጠልን ሳይካሄዱ ቀሩ የሚባሉ ጨዋታዎች መቀጠላቸው አይቀሬ ነው። ከንብረት ማውደም እስከ አካል ጉዳት ሲደርስ ታግሰናል። የሁንና ምትክ የሌለው የሰው ሕይወት በሥርዓት አልበኞች ሲጠፋ መመለከት አግባብነት የለውም። የሞት ዜና ከመምጣቱ በፊት አስፈላጊው መፈፀም አለበት። የሚቃጠለው እሳት ሳይዛመት የሚያጠፋው ይፈልጋል።

መሰል የወንድማማችነትና የመግባባት ምሳሌ የሆነውን ንፁህ እግር ኳስ የሚበክሉና ለስፖርታዊ ጨዋነት ግድፈቶች በዋነኛ ምክንያትነት የሚጠቀሱትን መለየት የግድ ይላል። በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ ሚዛናዊ ያልሆኑ ዘገባዎች መታረም አለባቸው። ስፖርታዊ ጨዋነት ለተጫዋች ተነስቶ ለዳኞች የሚተው ወይም ለደጋፊዎች ተነስቶ ለአሰልጣኞች የሚተው አይደለም። ሁሉም የቤት ሥራውን መሥራትና ጎርፉ ከመምጣቱ በፊት ቦዩን ማፅዳትና መሥራት ያስፈልጋል። «ከአምናው ካልተማርኩኝ ተመልሼ....» እንዳለው፤ አለመወሰናችን ነገም ከዚህም በላይ ዋጋ እንደሚያስከፍለን ጥርጥር የለውም።

 

ታምራት ተስፋዬ

Published in ስፖርት

ህይወት ላለው ፍጡር ሁሉ ውሃ ወሳኝ ነው፡፡ውሃ ሕይወት ነው መባሉም ለዚህም ነው:: ያለውሃ መኖር አይደለም መቆየት ያዳግታል:: ጤንነትን ጠብቆ ለመኖር ከሚያስችሉ እንዲሁም የብዙ በሽታዎች መፍትሄ ከሆኑት መካከልም ውሃ አንዱ ነው።

የህክምናው ዘርፉም ሰዎች በቀን ቢያንስ ሁለትና ከዚያ በላይ ሊትር ውሃ መጠጣት እንደሚያስፈልግ የሚመክሩ ትም ለዚህ ነው። ሆኖም ይህንን ምክር በተግባር የምንቀይር ስንቶቻችን ነን ቢባል ብዙዎ ቻችን ውሃ የመጠጣት ልምዱ ላይኖረን ይችላል። ውሃ ከመጠጣት በታቀብን ቁጥር በተለያዩ እንቅስቃሴዎቻችን በተለይም በጤናችን ላይ ችግር ሊከሰት ይችላል፡፡

ይህ ደግሞ ለ35 ዓመቱ ጀርመናዊ የበለጠ የከፋ ነው፡፡እኛ ውሃ ሳንጠጣ በቆየን ቁጥር ጉሮሯችንና ከንፈራችን መድረቅ ይጀምራሉ፡፡ሰውነታችን ይገረጣል፡፡ችግሩ እየከፋ ሲሄድ ደግሞ ሰውነታችን እየደረቀ እና እየደከመ ይመጣና ለሞት መዳረግም ሊከተል ይችላል፡፡

ኢዲቲ ሴንትራል ሰሞኑን ባስነበበው ዜና ጀርመናዊው ማርክ ውበንሆረስ ሰውነቱ በተፈጥሮው ለድርቀት የተጋለጠ መሆኑን ጠቅሶ፣ ውሃ ሳይጠጣ ለደቂቃዎች ከቆየ እስከ ሞት ሊያደርስ በሚችል ችግር ውስጥ እንደሚገባም ዘግቧል።

እንደ ዘገባው ውበንሆረስ ውሃ ቶሎ ቶሎ መጠጣት ከቻለ ሰውነቱ እንደ ማንኛውም ሰው ጤነኛ መሆን የሚችል ሲሆን፣ ውሃ ሳይጠጣ በቆየ መጠን ሰውነቱ እየገረጣ ከመሄዱ በተጨማሪ ኩላሊቱ ወዲያውኑ ሥራ የሚያቆም በመሆኑ ከአፉ ውሃ ሳይለይ በቀን እስከ 20 ሊትር ሲጠጣ ይውላል።

ውበንሆረስ በምንም መንገድ ቢሆን ለአንድ ሰዓት ያህል እንኳን ድርቀት እንዳለበት መርሳት የለበትም የሚለው ዘገባው ፣ይህንን ረሳ ማለት ግን የተለያዩ የድርቀት ስሜቶች ይገጥሙታል፤ብሎም እንደ ከንፈር መሰነጣጠቅ ፣ድብርትና አለመረጋጋት ያሉ ስሜቶች ያከተላሉ።

ይህ ሁኔታ የውበንሆረስን ህይወት እጅግ ከባድ አድርጎበታል፡፡ አንድም ጓደኛ የለውም፤ በተለይም ሌሊት የሚጠጣው ውሃ ሽንት ቤት መመላለስ የግድ እንዲሆንበት አድርጓል፡፡ ውበንሆረስ በ24 ሰዓታት ውስጥም ቢያንስ ለ50 ጊዜ ያህል መጸዳጃ ቤት መመላለስ አለበት፡፡ እስከ 35 ዓመት ዕድሜው ድረስ እፎይ ብሎ የተኛው ለ2 ሰዓታት ብቻ መሆኑም ጉዳዩን እጅግ አስገራሚ አድርጎታል። በዚህም የተነሳ ሥራን ጨምሮ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ቀድሞ መዘጋጀትና እቅድ ማውጣት ይኖርበታል። ድንገት የሚያደርገው አንዳችም ነገር እንደሌለ የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ ያመ ለክታል።

Published in መዝናኛ
Tuesday, 05 December 2017 17:58

‹‹ጨቋኟ ከተማ››

ወዳጆቼ ስለጨቋኝ ከተማ ቢወራልዎ እርግጠኛ ነኝ ከተማዋ በበርካታ ችግሮች የታጠረች፣መሰረተ ልማቷ በበቂ ሁኔታ ያልተሟላና ህዝቦች የሚጉላሉባትና የሚ ማረሩባት ከተማ ሳትሆን አይቀርም የሚል ግምት ሊያድርብዎት ይችላል፡፡ እርስዎ ይሄን ቢያስቡም የከተማዋ የጨቋኝነት ምስጢር ግን ሌላ ነው፡፡

በብዙ የዓለማችን ከተሞች የኛንም ጨምሮ ሰዎች አንድን ድርጊት እንዳይፈፅሙ የሚከለክሉ በርካታ ምልክቶች በየቦታው ተተክለው ተለጥፈው ወዘተ ይገኛሉ፡፡ከሰሞኑ ስካይ ኒውስ ለንባብ ያበቃው ፅሁፍ እንደሚያመለክተው፤ ዳውሊሽ የተሰኘችውና በደቡብ እንግሊዝ የባህር ዳርቻ አካባቢ የምትገኘው ከተማ በበርካታ ‹‹ ይህን ማድረግ ክልክል ነው!!›› በሚሉ ምልክቶች በመጨናነቋ በጎብኚዎች ዘንድ ‹‹ጨቋኟ ከተማ›› የሚል ስያሜን አትርፋለች፡፡

ከተማዋን ለመጎብኘት ዕድል ያጋጠመው በድረገፅ ላይ የሚፅፍ አንድ ግለሰብ በከተማዋ የተለጠፉት እና የተሰቀሉት ከልካይ ምልክቶችን ከታዘበ በኋላ ‹‹ፍፁም እንደ ልብ እንዳልንቀሳቀስ አግደውኛል›› ሲል በምሬት ገልጾታል፡፡

ዘገባው እንደሚያስረዳው፤ በከተማዋ ‹‹ወፎችን መመገብ ክልክል ነው!!››፣‹‹ውሻ ይዞ መንቀሳቀስ ክልክል ነው!!››፣ ‹‹ለዳክዬዎች ፍርፋሪ ዳቦ መመገብ ይመርዛቸዋል!!›› የሚሉና ሌሎችም ከልካይ ምልክቶች እጅግ የበዙ ከመሆኑ አንጻር ከተማዋን የጎበኘው የድረ ገፅ ፀሐፊ ‹‹ዳውሊሽ የድሮ ከተማ መስላለች፤ በበርካታ የክልከላ ምልክቶች ተጨናንቃለች በዚህም በጎብኚዎቿ ላይ የጭቆና ስሜት አሳድራለች፡፡›› ሲል ነበር የገለፀው፡፡ ጎብኚዎች ወደከተማዋ ሲመጡ የክልከላ ምልክቶቹን ከሚያዩ ይልቅ «በእንኳን ደህና መጣችሁ» መልዕክት መቀበል ያስፈልጋል። ሲልም ነው በጽሑፉ ላይ ያሳፈረው፡፡

በህይወት ዘመኑ ከጎበኛቸው ቦታዎች ሁሉ ይህች ከተማ የተለየች መሆኗን አመልክቶ፣ በዚህ ዓይነት የክልከላ ምልክት የተጨናነቀ ከተማም አጋጥሞት እንደማያቅም ጠቁሟል፡፡

የከተማዋ ከንቲባ አማካሪ ሚስተር ማረቲን ሪንግሊ በበኩላቸው በከተማዋ በርካታ የክልከላ ምልክቶች መኖራቸውን ተከትሎ ጎብኚዎች ቅሬታ እያስነሱ መሆኑን በመገንዘብ ምልክቶቹን በመቀነስ ከተማዋ በጎብኚዎች ዘንድ የተሻለ ተቀባይነት እንዲኖራት እንደሚሰራም ለስካይ ኒውስ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ከተማዋ ጨቋኝ ናት ለማለት አልደፍርም፤ይሁን እንጂ አንዳንድ የክልከላ ምልክቶችን በመቀነስና በተሻሉ ቃላት ቀይሮ በመፃፍ ለማስተካከል ጥረት ይደረጋል ሲሉም የከንቲባው አማካሪ ተናግረዋል፡፡

 

አስናቀ ፀጋዬ

Published in መዝናኛ

ኢህአዴግ እና 15 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም በሁለት አጀንዳዎች ላይ ተደራ ድረው ለማሻሻል ከስምምነት ደርሰዋል፡፡ ከእነዚህ ድርድር ከተካሄደባቸው አጀንዳዎች መካከል የምርጫ ሥነ ሥርዓት ላይ የተደረገው ይጠቀሳል፡፡ ፓርቲዎቹ ህዳር 14 ቀን 2010 ደግሞ ሦስተኛ አጀንዳ በሆነው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ 662/2002 ላይ ተደራ ድረዋል፡፡ በድርድሩም ተቃዋሚዎች መሻሻል፣ መሰረዝ እና መጨመር አለባቸው ያሏቸውን አንቀጾች እና ንዑስ አንጾች አቅርበው ተወያይተዋል፡፡

ለድርድሩ አመቺነት ሲባል አሥራ አንድ ፓርቲዎች የድርድር ሃሳባቸውን በጋራ ያቀረቡ ሲሆን፣ መኦህዴፓ በአዋጁ ላይ የመደራደሪያ ነጥብ የለኝም ቢልም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚያቀርቡት የመደራደሪያ ነጥቦች ላይ የድጋፍ እና የተቃውሞ ድምጽ አሰምቷል፡፡ ኢህአዴግ በአዋጁ ላይ የማሻሻያ ሃሳብ ባያቀርብም፣ ተደራዳሪ ፓርቲዎች ባቀረቧቸው የመደራደሪያ ነጥቦች ላይ ተደራድሯል፡፡

የአዋጁ ምንነት እና የድርድሩ አስፈላጊነት

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ከ2002 ሀገራዊ ምርጫ በፊት አዋጅ 662/2002 በሚል የወጣ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አዋጁ የጸደቀው ከሁለት ወራት ድርድር በኋላ ነው፡፡ተደራዳሪዎቹ ኢህአዴግ፣ ቅንጅት፣ ኢዴፓ እና መኢአድ ቢሆኑም በማጽደቅ ላይ ግን በርካታ ፓርቲዎች ተሳትፈዋል፡፡ 39 አንቀጾችን ያቀፈው ይህ አዋጅ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ፓርቲዎች ድርድር የተጀመረበት ነው ሲሉ አንዳንድ ወገኖችም ጉዳዩን ይገልጹታል፡፡

በአዋጁ መግቢያ ላይ እንደተመለከተው፤ ከ2002 በፊት በሀገሪቱ ከተካሄዱ ምርጫዎች ትምህርት በመውሰድ ወደፊት የሚካሄዱ ምርጫዎች በመልካም ሥነምግባር የሚመሩ ግልጽ፣ ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊ፣ ህጋዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እንዲሁም በህዝብ ተቀባይነት ያላቸው እንዲሆኑ ለማስቻል በምርጫ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እጩዎች፣ የፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች የሚመሩበት ዝርዝር የሥነ ምግባር ህግ ማውጣት አስፈላጊነት አዋጁ እንዲወጣ ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡

አዋጁ የጸደቀው ጊዜ ተወስዶ በፓርቲዎች መካከል ብዙ ክርክሮች ከተደረገበት በኋላ ነው፡፡ፖለቲካ በኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ምክንያቶች የሚቀያየር ሲሆን፣ የቴክኖሎጂው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቀቀ መሄድም ሌላ ምክንያት ይሆናል፡፡ በመሆኑም ከዓመታት በፊት የወጡ አዋጆችን፣ ደንቦችን እና መመሪያዎችን በአሁኑ ወቅት ለመተግበር አዳጋች ሲሆን ይታያል፡፡

በተለያዩ ሀገራት ከምርጫ ህግ ጎን ለጎን የሚተገበር የፓርቲዎች ሥነ ምግባር ደንብ ያለ በመሆኑ በአዋጁ አስፈላጊነት ላይ አብዛኞቹ ፓርቲዎች እምነቱ አላቸው፡፡ በመሆኑም ይህን አዋጅ ለወቅቱ የሚመጥን ማድረግ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡የአዋጁን ድክመቶች ነቅሶ በማውጣት አዋጁን ማሻሻልም ያስፈለገው ለዚህ ነው፡፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች ለድርድር ከቀረቡ ሃሳቦች በከፊል

መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ ቅንጅት፣ መኢዴፓ፣ ኢብአፓ፣ አንድነት፣ ኢዲአን፣ ኢድህ፣ አትፓ፣ ኦህዴፓ እና እሶዴፓ በጋራ የድርድር ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ የእነዚህን አሥራ አንድ ፓርቲዎች ሃሳብ ያቀረቡት የአንድነት ፕሬዚዳንት አቶ ትዕግስቱ አወል እንደተናገሩት፤ አዋጁ ከሀገሪቱ አዋጆች ሁሉ ይለያል፡፡ የሌሎች አዋጆች ረቂቅ የሚቀርበው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲሆን፣ የዚህ አዋጅ ረቂቅ የቀረበው ግን በፓርቲዎች ስምምነት መሆኑ የተለየ ያደርገዋል፡፡ይህ አዋጅ የተለየ ልምድ የወለደም እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ልዩ ባህሪ መገለጫ ነው፡፡

በፓርላማ መቀመጫ የሌላቸው ፓርቲዎች ጭምር በጋራ ምክር ቤት አማካይነት በፖሊሲ ላይ ሊወያዩ የሚችልበት ዕድል የፈጠረ አዋጅ መሆኑን በመጥቀስም ፣በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተሰራበትም አቶ ትዕግስቱ ይናገራሉ፡፡አዋጁ እንዲሻሻል የአሥራ አንዱም ፓርቲዎች እምነት ነው፡፡

በዚሁ መሰረት አቶ ትዕግስቱ አሥራ አንድ የሚሻሻሉ፣ አራት የሚሰረዙ እና ሁለት የሚጨመሩ፤ በአጠቃላይ አሥራ ስድስት ነጥቦችን አቅርበዋል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ ‹‹ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በሚመለከተው ህጋዊ አካል የተረጋገጠን የምርጫ ውጤት መቀበል አለበት›› የሚለው መሻሻል ካለባቸው አንቀጾች አንዱ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የምርጫ ውጤቱ በቦርዱ ከመገለጹ ቀደም ብሎ ታዛቢዎች ስለምርጫው አጠቃላይ ሁኔታ ሃሳባቸውን የሚሰጡበት ዕድል ሊፈጠር ይገባል፡፡ ታዛቢዎቹ ይህን የሚያደርጉ ከሆነ ለቦርዱም እገዛ የሚኖረው ከመሆኑ ባሻገር የምርጫ ውጤት ተዓማኒነት እንደሚጨምር ይናገራሉ፡፡ ‹‹ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በውጭ እና በሀገር ውስጥ ታዛቢዎች ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ፣ ነጻ መሆኑ የተመሰከረለትን የምርጫ ሂደት በምርጫ ቦርድ የተረጋገጠ የምርጫ ውጤት መቀበል፣የምርጫው ውጤት በቦርዱ ይፋ ከሚደረግበት ቀን በፊት የታዛቢዎቹ ሃሳብ መቅረብ አለበት›› በሚል ቢሻሻል የሚል ሃሳብ አቅርበዋል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ 4 የምርጫ አስፈጻሚዎች በጋራ ምክር ቤት ውይይት ላይ እንደማይገኙ ነገር ግን የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ ተስማምቶ እንዲገኙ ከወሰነ ያለድምጽ በስብሰባው ላይ መገኘት እንደሚችሉ የተቀመጠውም እንዲሻሻል ጠይቀዋል፡፡

በሙሉ ድምጽ የሚለው ተገቢነት እንደሌለው የገለጹት አቶ ትዕግስቱ፣ ይህ ከሆነ አብዛኞቹ ፓርቲዎች የተስማሙበትን እንኳን አንድ ፓርቲ ብቻውን ሊያፈርስ የሚችልበትን እድል ይፈጥራል፡፡ ይህ አንቀጽ ‹‹በየደረጃው የሚገኙ ምርጫ አስፈጻሚዎች እንደ አስፈላጊነቱ በውይይት ላይ እንዲገኙ በጋራ ምክር ቤቱ አባላት በስምምነት ወይም በ2/3ኛ ድምጽ ሲወሰን ያለ ድምጽ ይሳተፋሉ›› ተብሎ እንዲሻሻል የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይ የጋራ ምክር ቤት ውሳኔ የሚተላለፈው በጋራ መግባባት ወይም በተባበረ ድምጽ እንደሚሆን የሚደነግገው አንቀጽ 26/ 11 ‹‹የጋራ ምክር ቤት ውሳኔ የሚተላለፈው በጋራ መግባባት ወይም በ2/3ኛ ድምጽ ይሆናል›› በሚለው ቢሻሻል የተሻለ እንደሆነ ሃሳብ ቀርቧል፡፡

በምርጫ ህጉ መሰረት በቦርዱ የሚመሰረተው የፓርቲዎች መድረክ እንደተጠበቀ ሆኖ የጋራ ምክር ቤት ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ምርጫ ክልል ድረስ እንዲቋቋም እንደሚደረግ የሚደነግገው አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 2 በደፈናው ይቋቋማል ይላል እንጂ ይህን ተግባር የመፈጸም ኃላፊነት የማን እንደሆነ ግልጽ አላደረገም፡፡ ይህ ተቋም ያቋቁማል የማይል በመሆኑ ለአሻሚ ትርጉም ያጋልጣል፤ በመሆኑም ‹‹የጋራ ምክር ቤቶች ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ምርጫ ዞን ድረስ የማቋቋም ኃላፊነት የምርጫ ቦርድ ይሆናል›› በማለት ኃላፊነቱ የሚመለከተውን አካል መጥቀስ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል፡፡

አራት አንቀጾች እንዲሰረዙ በአሥራ አንዱ ፓርቲዎች ስብስብ ሃሳብ የቀረበ ሲሆን፣ ለአዋጅ ተገዥ ስለመሆን እና ህግን ስለማክበር የተቀመጡት አንቀጽ 6 እና 7 አላስፈላጊ ናቸው፡፡ ምክንያቱም በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ በፌዴራል የወጡ ህጎች ሁሉ መቀበል ግዴታ መሆኑ ስለተደነገገ እነዚህ አንቀጾች ድግግሞሽ ስለሆኑ መሰረዝ አለባቸው ይላሉ፡፡

አንቀጽ 16/3 የግል እጩዎችን በተመለከተ የጋራ ምክር ቤቱ የሚደራጀው በፓርቲዎች በመሆኑ የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች በታዛቢነት መገኘታቸው ቀጣይነት ስለሌለው እና አዋጁም ስለማይመለከታቸው ቢሰረዝ የሚል ሃሳብም አቅርበዋል፡፡ እንዲሁም በአንቀጽ 21/7 ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥነ ምግባር አዋጅ ሲቀረጽ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ያልተሳተፉ ሌሎች ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ አባል ለመሆን የጋራ ምክር ቤቱ የሚያወጣውን የስምምነት ሰነድ መፈረም እንዳለባቸው የሚደነግገው ‹‹በየደረጃው ለተቋቋሙ የጋራ ምክር ቤቶች አባል ለመሆን የሚጠይቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቶቹን መተዳደሪያ ደንብ ተቀብለው የስምምነት ሰነድ መፈረም ይኖርባቸዋል›› በሚል እንዲሻሻል ሃሳብ ቀርቧል ፡፡

የአሥራ አንዱን ፓርቲዎች ሃሳብ ያቀረቡት አቶ ትዕግስቱ መሻሻል እና መሰረዝ አለባቸው ካሏቸው አንቀጾች ባሻገር መጨመር ያለበትንም ሃሳብ ጠቁመዋል፡፡ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ እንዲጎለብት ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በሚያተኩሩ መድረኮች ላይ ተሳታፊ በመሆን የሚል ሃሳብ በአንቀጽ 22 ስር መካተት አለበት ብለዋል፡፡

የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ በበኩሉ በገዳ ስርዓት መሰረት የሀገሪቱ ምርጫ በየአራት አራት ዓመቱ እንዲሁም የአስፈጻሚ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ እንዲሆን በማለት የማሻሻያ ሃሳብ አቅርቧል፡፡አዋጁ በራሱ የፓርቲዎች ሥነ ምግባር አዋጅ በሚል መሻሻል አለበት የሚል ሃሳብም አቅርበዋል፡፡ ምክንያቱም ፓርቲዎች በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ስለሚወያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥነ ምግባር አዋጅ በሚል ይሻሻል የሚል ሃሳብ ፓርቲው ካቀረባቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በዚሁ ንዑስ አንቀጽ // ላይ ‹‹የጋራ ምክር ቤቱ አባል የሆኑ ፓርቲዎች እያንዳንዳቸው ለጋራ ምክር ቤት የሚወ ክሏቸው አባላት ቁጥር የጋራ ምክር ቤቱ በሚያወጣው የመተዳደሪያ ደንብ ይወሰናል›› በሚለው ላይ የፓርቲዎቹን መሪዎች ጨምሮ ፓርቲዎቻቸው በሚወክሏቸው ከፍተኛ አመራሮች የሚወሰን ይሆናል›› የሚል እንዲታከልበት ቀርቧል፡፡

በአንቀጽ 21/2/ሀ ምክር ቤቱ በክልል ለምርጫ ውድድር በተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይመሰረታል የሚለው በሀገር አቀፍ፣ በክልል እና በዞን ደረጃ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ተመዝግበው የምስክር ወረቀት ባላቸው ፓርቲዎች ይመሰረታል በሚል መሻሻል አለበት፤ ምክንያቱም ያኛው ፓርቲዎችን የሚከፋፍል እና የሚነጣጥል በመሆኑ መስተካከል አለበት፡፡

የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ተደራዳሪዎች በበኩላቸው አዋጁ ለሀገሪቱ ፖለቲካ ካስገኘው ጥቅም አንጻር የሚሞካሽ አለመሆኑን በመግለጽ ሃያ አንድ አንቀጾችና ንዑስ አንቀጾች እንዲካተቱ የድርድር ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ አዋጁ በርካታ ችግሮች ያሉበት መሆኑንም እንዲሁ አመልክቷል፡፡ ለአብነት ያህል የጋራ ምክር ቤትን በተመለከተ አዋጁ ያስቀመጠው አንቀጽ በራሱ የከፋፋይነት ባህሪ ያለው ነው፡፡ በመሆኑም በምክር ቤቱ የተለያዩ ርዕዮተ ዓለም ያላቸውን ፓርቲዎች በአንድ ጥላ ስር ለመሰብሰብ አዋጁ ምንም የፈየደው የለም፡፡ አዋጁ ፓርቲዎችን አደፋፋሪ ሳይሆን ገፊ ነው፡፡ በመሆኑም የአዋጁ ፋይዳ እምብዛም ነው ብሏል፡፡ በመሆኑም መሻሻል ያለበት ተሻሽሎ፣ መሰረዝ ያለበት ተሰርዞ እና መጨመር ያለባቸው አንቀጾች ተካተው ለወቅቱ በሚመጥን መልኩ ሊስተካከል ይገባል ሲል ሀሳቡን አቅርቧል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 21 ላይ የሰፈሩት ሀሳቦች ፓርቲዎችን የሚከፋፍል እና አብረው እንዳይሰሩ የሚያደርጉ ከመሆናቸውም ባሻገር እርስ በርስ የሚያፋጁ ሃሳቦች ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል በዚህ አንቀጽ ስር የጋራ ምክር ቤት በሀገር አቀፍ ለምርጫ ውድድር በተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚመሰረት የሰፈረው አንቀጽ ተጠቃሽ ነው፡፡ የትኛውም ፓርቲ በፍላጎት እና በነጻነት መርህ ላይ ተመስርቶ ከጋራ ምክር ቤት የመግባትም ሆነ የመውጣት መብትን በሚያስጠብቅ መልኩ ሊደነገግ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እንደዚህ ዓይነት የሚያራርቁ ሃሳቦች ደግሞ ቢያንስ በህግ ደረጃ ሊኖሩ አይገባም፡፡ በመሆኑም በፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ ተመዝግበው የምስክር ወረቀት ባላቸው ፓርቲዎች እንዲመሰረት የሚደነግግ ህግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በመድብለ ፖርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ስለሚመረጥ መንግሥት በአንቀጽ 5 ላይ የሰፈረው ይህ ድንጋጌ በምርጫው ሂደት እና ምንነት፣ ተሳትፎ እና ውጤት ላይ ልዩ ነጥብ ያሳርፋል፡፡ የአንድ ፓርቲ የመንግሥትነት ህጋዊነት የሚረጋገጥበት ተብሎ የተቀመጠው ሃሳብ በጣም ቁንጽል እና ጠባብ ነው፡፡ በምርጫ ወቅት ለ24 ሰዓታት ብቻ ተግባራዊ በሚሆን ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ያሉት አመራሮቹ፣ መራጮች በምርጫ ዘመቻ አማካይነት ብቻ በሚከናወኑ ነጥቦች ህጋዊ መሆኑ ለአንድ መንግሥት ህጋዊነት በመርህ ደረጃ በቂ ነው ብለን እንድንቀበል ያስገድዳል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

በመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚመረጥ መንግሥት ህጋዊነት የሚረጋገጥበት ሌሎች ነጥቦች ልጨመሩ ይገባል፡፡ የድህረ ምርጫውም ሆነ ቅድመ ምርጫው ሂደት ግልጽ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ፣ ህጋዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንከን የለሽ በሆነ ምርጫ ህዝባዊ አመኔታ ባለው መልኩ ህጋዊ ተቀባይነት ያገኘ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ህጋዊ ቅቡልነትና ህዝባዊ አመኔታ የሌለው፣ ግልጽ፣ ፍትሃዊ እና ሰላማዊ ያልሆነ፤ በምርጫ ዘመቻና ምርጫ ሂደት ላይ ብቻ በተንጸባረቁ የተወሰኑ አዎንታዊ ጎን በሚመስሉ ጉዳዮች ብቻ ስልጣን ላይ የተቀመጠን ፓርቲ ህጋዊ ነው ብሎ መቀበል ያስቸግራል፡፡

ስለዚህ በመድብለ ፓርቲ የዴሞክራሲ ሥርዓት የሚመረጥ መንግሥት ህጋዊነት የሚመሰረተው በቅድመ ምርጫና ድህረ ምርጫ ያሉ ሂደቶች ነጻ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ህጋዊ በሆነ መንገድ እንከን የለሽ በሆነ ምርጫ የተመረጠ መሆኑን የሚጠቅስ አንቀጽ አዋጁ ላይ ማካተት ያስፈልጋል፡፡ በሚገኘው የምርጫ ውጤት ላይ ሙሉ በሙሉ መተማመኛ ያለው መንግሥት መሆን እንዳለበትም የኢራፓ ተደራዳሪዎች ጠቁመዋል፡፡

አዋጁ የጋራ ምክር ቤት ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ምርጫ ክልል እንደሚቋቋም ይደነግጋል፡፡ ሆኖም የሀገር አቀፍ ፓርቲዎች እና የክልል ፓርቲዎች በምን ደረጃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚችሉ በግልጽ አልተቀ መጠም፡፡ ስለዚህ የክልል እና የፌዴራል ፓርቲዎች የሀገር አቀፍ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤት ላይ እንደሚሳተፉ በግልጽ መቀመጥ እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

የመላው ኢትዮጵያውያን ብሄራዊ ንቅናቄ (መኢብን) በበኩሉ አሥር አንቀጾች እና ንዑስ አንቀጾች እንዲሻሻሉ ሃሳብ አቅርቧል፡፡ በየሴክተር መስሪያ ቤቱ የልማት ሠራዊት ተብለው የሚቋቋሙ አደረጃጀቶች በምርጫ ላይ በተለያዩ አኳኋኖች ሲሳተፍ ይስተዋላል፡፡ ይህ ደግሞ በምርጫ ላይ ችግር ሲፈጥር ይታያል፡፡ በዚህ አዋጅ ላይ እነዚህ አደረጃጀቶች በምንም መልኩ ምርጫ ላይ ተሳታፊ እንዳይሆኑ የሚደነግጉ አንቀጾች ሊካተቱ ይገባል የሚለው ካቀረባቸው ሃሳቦች መካከል ይጠቀሳል፡፡

ኢህአዴግ ምን አለ

የኢህአዴግ ዋና ተደራዳሪ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ይህ አዋጅ ኢህአዴግ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ረጅም ጊዜ ወስደው ከተደራደሩ በኋላ ህግ ሆኖ ወጥቷል፡፡ በአዋጁ ላይ ኢህአዴግ ለድርድር የሚያቀርበው ሃሳብ የለውም፡፡ አቶ ሽፈራው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ካቀረቧቸው ሃሳቦች መካከል የተወሰኑትን ውድቅ አድርገው፣ ሃሳቦቹ ግን ጠቃሚ መሆናቸውን አቶ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡ እነዚህ አንቀጾች በሕግ አሠራር ታይተው ሊሻሻሉ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡

ስለ ምርጫ ውጤት ታዛቢዎች ሊኖራቸው ስለሚገባው ሚና ከፓርቲዎች ለተነሳው የማሻሻያ ሃሳብ በሰጡት አስተያየት ታዛቢዎች ሚናቸው የምርጫ ሂደትን መገምገም ነው፡፡ ታዛቢዎች ሥራቸው የምርጫው ሂደት ፍትሃዊ እና ነጻ ስለመሆኑ መታዘብ ነው፡፡ ውጤት መግለጽ አይደለም፡፡ አንቀጹ ደግሞ የሚያስረዳው ውጤትን ስለመቀበል ነው፡፡ ውጤት የመግለጽ ኃላፊነት ደግሞ ያጫወተው አካል ወይም የዳኛ ነው፡፡ ዳኛው ደግሞ ታዛቢ ሳይሆን የምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሃሳብ መነሳት የሌለበት በመሆኑ ሃሳቡን እንዲተውት ጠይቀዋል፡፡ በሌሎች ሀገራትም ቢሆን የምርጫ ውጤትን የሚያሳውቀው የምርጫ ቦርድ ወይም ኮሚሽን መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የታዛቢዎች የምርጫ ውጤት መግለጽ በምርጫ ውጤት ተዓማኒነት ላይ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል አቶ ሽፈራው ይናገራሉ፡፡ታዛቢዎች ለአንድ ወገን ሊያደሉ እንደሚችሉ በመጥቀስም በታዛቢዎች የሚገለጽ ውጤት ተዓማኒ ሊሆን እንደማይችል ያብራራሉ፡፡ ለአብነት ያህል በቅርቡ በኬኒያ በተደረገው ምርጫ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ታዛቢዎች ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ እንደነበር ቢገልጹም ምርጫው የተደገመበትን አጋጣሚ ጠቅሰዋል፡፡

የጋራ ምክር ቤት ከፌዴራል እስከ ምርጫ ክልል መኖር አለበት በሚል ከፓርቲዎቹ የተነሳው ጥያቄ ተገቢነት ያለው ነው ያሉት ዋና ተደራዳሪው ፣ በዞንም ሆነ በምርጫ ክልል ምክር ቤቶች መቋቋም ላይ ኢህአዴግ ልዩነት እንደሌለው ያመለክታሉ፡፡

አንዳንድ ለድርድር የቀረቡ ሃሳቦች የአፈጻጸም ችግሮች እንጂ የአንቀጾቹ ችግር አለመሆናቸውንም የጠቀሱት አቶ ሽፈራው፣ በአፈጻጸም ችግሮች ላይ በማውራት ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ሌሎች መዋቅሮችን ማበጀት ለአላስፈላጊ የገንዘብ ወጪ ይዳርጋል ይላሉ፡፡በአፈጻጸም ችግሮች ላይ በመወያየት ማስተካከል እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

መኢብን ላቀረበው ሃሳብ በሰጡት አስተያ የትም በተለያዩ የልማት ሠራዊቶች ውስጥ የኢህአዴግ አባላት ካሉ በምርጫ ጊዜ ቅስቀሳ ላይ ይዘምታሉ፡፡ የልማት ሠራዊት የሆነ ሰው ሁሉ ኢህአዴግ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ የተለያዩ ፓርቲዎች አባል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አባል ለሆኑበት ፓርቲ መቀስቀስ ግን ሊከለከሉ አይገባም ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ምርጫው በየአራት ዓመቱ እና የአስፈጻሚ ምርጫ በየስምንት ዓመቱ እንዲካሄድ በማለት የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ ያቀረበውን ሃሳብም በሁለት ምክንያች ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡ የገዳ ስርዓትን በሚያራምደው በኦሮሞ ብሄር ዘንድ ምርጫ የሚካሄደው በየስምንት ዓመቱ እንጂ በየአራት ዓመቱ አለመሆኑን በመግለጽ ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ የህዝብን ባህል ማዛባት ተገቢነት እንደሌለው አቶ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡ አዋጁ የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚተዳደርበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

 

መላኩ ኤሮሴ

 

 

Published in ፖለቲካ
Tuesday, 05 December 2017 17:34

የወርቅ ግብይት ማበረታቻ

 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ የወርቅ ግዥ በማከናወን ወደ ውጭ አጓጉዞና አስነጥሮ በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ሂሳብ ገቢ ሲያደርግ ቆይቷል። ባንኩ በአገር ደረጃ ሥራውን በማሻሻል የወርቅ ግብይት ህጋዊ በሆነ አሰራር እንዲከናወን የተለያዩ ፖሊሲዎችን በመንደፍ ተግባራዊ ሲያደርግ መቆየቱን ባንኩ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

1. በባህላዊ መንገድ በወርቅ አምራቾች ተመርቶ በማእከል ደረጃ ለባንኩ ሲቀርብ የነበረው ወርቅ የአቅራቢዎች ቁጥር በመጨመሩ እንዲሁም የወርቅ ግብይቱን ሥራ በአንድ የግዥ ማእከል ብቻ በማከናወን የአቅራቢዎችን ፍላጎት ማርካት ባለመቻሉ በክልሎች የግዥ ማእከላት ተከፍተው ግብይቱ እንዲከናወን ያደረገበት አሰራር አንዱ ነው፡፡ በዚህም አቅራቢዎች ረጅም መንገድ ሳይጓዙ የያዙትን ወርቅ ባሉበት አካባቢ እንዲሸጡ የአሰራር ለውጥ በመደረጉ ወርቅ አቅራቢዎች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

የወርቅ ግብይትን የወርቅ ማዕድን በብዛት ወደሚገኝባቸው አካባቢዎች ማስፋፋቱ ነጋዴዎች ወርቁን ወደ ማዕከል ለማጓጓዝ ይከፍሉ የነበረውን የትራንስፖርትና ተያያዥ ወጪዎች በመቀነስ እና ሥራውን በማሻሻል የበለጠ ተበረታተው ያመረቱትን ወርቅ ለባንኩ እንዲያቀርቡ ታስቦ የተደረገ ነው፡፡

2. ባንኩ የወርቅ ግዥ የሚፈጽመው በዓለም አቀፍ የወርቅ ዋጋ ላይ ተጨማሪ ከፍያ በማድረግ ነው፡፡በዚህም አቅራቢዎችን በማበረታታት ወርቅ በብዛት ለባንኩ እንዲቀርብ የሚያስችል የፖሊሲ እርምጃ ወስዷል፡፡በዚሁ ግንዛቤ ቀደም ሲል ሲሰጥ ከነበረው የዋጋ ጭማሪ 1 በመቶ እና 3 በመቶ ወደ 5 በመቶ ከፍ በማድረግ ተጨማሪ ክፍያ በእያንዳንዱ ግዥ ላይ ለነጋዴዎች እየተከፈለ እንዲሰራ መደረጉን ባንኩ ይገልጻል፡፡

3. ቀደም ሲባል በፖሊሲ በተቀመጠው መሰረት ነጋዴዎች ለባንኩ ወርቅ ሲያቀርቡ በወሩ ውስጥ በተመዘገበው ከፍተኛ የወርቅ ዋጋ ተሰልቶ ክፍያ እንዲያገኙ ሰፊ የዋጋ መምረጫ ጊዜ ይሰጥ ነበር፡፡በወቅቱ የወርቅ ክፍያ እየተፈጸመ የነበረው ወርቁ ለባንኩ ገቢ ከተደረገ በኋላ ሊኖር በሚችለው የወሩ ከፍተኛ ዋጋ ታስቦ ስለነበር የወርቁን እውነተኛ ዋጋ አያመለክትም ነበር፡፡ ይህም በመሆኑ ለወርቅ አቅራቢዎች ሲከፈል የነበረው ገንዘብ በአጠቃላይ ድምር ውጤት ሲታይ በጣም ከፍተኛ ስለነበር ባንኩን ለኪሳራ በመዳረጉ እንዲቀር ተደርጎ እንደነበር ባንኩ አስታውሷል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች የወርቅ አቅርቦት እየቀነሰ በመምጣቱ መንግሥት አቅራቢዎችን በማበረታታት ከዘርፉ መገኘት የሚገባውን አገራዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ መወሰኑን አስታውሶ፣ ቀደም ሲል ተግባራዊ ተደርጎ ነገር ግን የወርቅ ዋጋ መውረዱን ተከትሎ በተከሰተው ኪሳራ ምክንያት የተነሳውን የ30 ቀናት የዋጋ መምረጫ ማበረታቻ እንደገና ተግባራዊ እንዲሆን መደረጉን አስታውቋል፡፡

4. እላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ዝቅተኛ የቅበላ መጠን ከ150 ግራም ወደ 50 ግራም ፣ዝቅ በማድረግ ዝቅተኛ የፋይናንስ አቅም ያላቸው አምራቾች /አዘዋዋሪዎች ያመረቱትን ወይም የያዙትን ወርቅ በአቅማቸው ለባንኩ የሚያቀርቡበት አሰራር ተመቻችቷል፡፡ በተወሰነው መሰረት እላይ የተጠቀሱት ማበረታቻዎች ከጥቅምት 4 ቀን 2010 አም ጀምሮ በእያንዳንዱ ወርቅ ግዥ ማእከል ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኙ ያመለክታል፡፡ በመሆኑም ወርቅ አምራቾች እና አቅራቢዎች በየክልሉ በሚገኙ የወርቅ ግዥ ማእከላት በመቅረብ ያመረቱትን ወይም አዘዋዋሪዎች ከሆኑም ከአምራቾች የገዙትን ወርቅ ለባንኩ በመሸጥ ከማበረታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ባንኩ ያስታውቃል፡፡

 

በጋዜጣው ሪፖርተር

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ኢትዮጵያ ፣የሀገሪቱን የመንገድ ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ያስቻሉና የህብረተሰቡን የመንገድ ጥያቄ የመለሱ በዚህ ሁሉ ውስጥ ለዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ተግባሮችን እያከናወነች ትገኛለች፡፡ከዚህ አንጻር በከተሞች እየተካሄደ የሚገኘው የኮብል ስቶን መንገድ ሥራ በአብነት ይጠቀሳል፡፡በኮብል ስቶን የመንገድ ሥራው የሀገሪቱ ከተሞች መሰረታዊ የሆነው የመንገድ ችግር እየተፈታ ሲሆን፣መንገዶቹ በውበት በኩልም የሚወደዱ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ እየመሰከሩ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ኮንስትራክሽን ቢሮ ‹‹ለጉልበት ሠራተኞች የሥራ ዕድል በመፍጠር የዘላቂ ልማት ግቦችን ማሳካት›› በሚል መሪ ቃል በቅርቡ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተካሄደው አህጉራዊ ጉባዔ ላይ ያቀረበው ጽሁፍ እንዳ መለከተው፤ከተማዋ የኮብልስቶን መንገዶችን ለመገንባት በመጀመሪያ ሀሳቡ ሲጠነሰስ ባለሙያዎች ሳይቀሩ ግንባታውን ተቃውመውት ነበር፡፡ ባለሙያዎቹ መንገዱን የ17ኛው ክፍለ ዘመን ዓይነት እና ለዚህ ዘመን የማይመጥን በማለት አጣጥለውት ነበር፣ለአዲስ አበባ ከተማ የማይመጥንና ለእግረኞችም ሆነ ተሽከርካሪ ለሚጠቀሙ ነዋሪዎችም ምቾት የማይሰጥ ተብሎም እንደነበር አስታውሷል፡

ጽሁፉን ያቀረቡት የከተማዋ የኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው መንገዱ ተቃውሞ ቢገጥመውም አንዳንድ ነዋሪዎች ፍላጎት ማሳየታቸውን፣ይህም ለሙከራ ፕሮጀክትነት ተመርጦ ወደ ሥራ እንደተገባም ይገልጻሉ።እነዚህ ፕሮጀክቶች እንደተጠናቀቁም የከተማ አስተዳደሩ የማህበረሰቡን ተወካዮች በሙሉ በመያዝ መንገዱን ያስገነቡ ነዋሪዎች ያደረጉትን ጥረት ማስጎብኘቱን ይገልጻሉ፡፡

ኢንጂነሩ እንዳሉት፤የህብረተሰቡ ተወካዮች የድንጋይ ማምረቱን ማስዋቡንና ማንጠፉን ሥራ እንዲሁም የተገነቡትን መንገዶች ከተመለከቱ በኋላ ፍላጎታቸው በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይመጣል፤ይሁንና የነዋሪዎቹ የኮብልስቶን መንገድ ፍላጎትና የኮብልስቶን ድንጋይ አቅርቦት የሚመጣጠን ሳይሆን በመቅረቱም ለአስተዳደሩ ሌላ የቤት ሥራ ይፈጠራል ፡፡

ኢንጂነሩ እንዳመለከቱት፤ህብረተሰብን ባሳተፈ መልኩ በተከናወነው ርብርብ ሁለት ሺ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮብልስቶን መንገድ የተገነበ ሲሆን፣በዚህም ከስምንት ዓመታት በፊት ከ10 በመቶ በታች የነበረውን የከተማዋ የመንገድ ሽፋን በአሁኑ ወቅት ወደ 18 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡

የመንገድ ሥራው ለበርካታ የከተማዋ ወጣቶች የሥራ ዕድል ማስገኘት የቻለ ሲሆን፣ባለፉት ስምንት ዓመታት በዚህ የመንገድ ሥራ ከ170 ሺ በላይ ወጣቶች ለመንገድ ሥራው የሚያገለግል ድንጋይ ማምረትና በኮብልስቶን አዘገጃጀት ስልጠና ወስደው በመንገድ ግንባታ ተሰማርተው ገቢያቸውንም አሳድገዋል፡፡

በከተማዋ የኮብልስቶን መንገድ ሥራ ከተጀመረበት ከ2003 አንስቶ ለኮብልስቶን አምራቾች 7 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ በመንገድ ሥራው የተሳተፉ ወጣቶች በእነዚህ ዓመታት ሁለት ቢሊዮን ብር የሚሆን በመቆጠብ ወደ ሌላ ሥራ ዓይነት ለመሸጋገር የሚያስችላቸውን ጥሪትም ማፍራት ችለዋል፡፡

የመንገድ ሥራው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው እንደመሆኑም ወጣቶቹ የቆጠቡት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይም ሀገሪቱ ቁጠባን ለማሳደግ እያደረገችው ለምትገኘው ተግባር የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ሲጀመር ታቃውሞ ገጥሞት የነበረው የኮብልስቶን መንገድ ሥራ ህዝቡ በመንገዶቹ መርካቱ በተለያዩ ግምገማዎች መረጋገጡን ጽሁፉ አመልክቷል፡፡ መንገዶቹ በመሬት አጠቃቀም ላይ እሴት መጨመር ችለዋል፣መንገዶቹ የተገነቡባቸው መስመሮች የንግድ እንቅስቃሴ እየጨመረ እንዲመጣ አድርገዋል፡፡በዚህ እና በመሳሰሉት የሚፈጠረው የሥራ ዕድልም ከፍተኛ ሆኗል፡፡የአካባቢው ጽዳት የተጠበቀ እንዲሆን ከማድረግ በተጨማሪ አረንጓዴ ሥፍራዎችን ለማልማትም ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ነዋሪዎች በተሽከርካሪ ከመሄድ ይልቅ በእግር ሊንቀሳቀሱባቸው የሚመርጧቸው ሆነው ተገኝተዋል፡፡

በተያዘው የፈንጆቹ ዓመት ባለፉት አስር ወራትም 100 አነስተኛ እና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ተቋቁመው በህብረተሰብ ተሳትፎ በሚከናወኑ ሥራዎች በተለይም ለኮብልስቶን መንገድ ሥራ በሚካሄዱ ግንባታዎች እየተሳተፉ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

 

መላኩ ኤሮሴ

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የሐራሬው አብዮት አስግቷቸዋል፤

 

አንዳንድ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ወደ ስልጣን ሲመጡ የሚታየው የህዝብን እውቅና አግኝተው ወይም በህዝብ ድምጽ ተመርጠው ሳይሆን በመፈንቅለ መንግስት፤ በጦርነት ሀይል ስልጣንን በመቆጣጠር አሊያም በዘር ውርስ የስልጣን ርክክብ በማድረግ ነው።

በዚህ ሂደት ወደ ስልጣን የመጡ መሪዎችም አንዴ የመሪነትን ሃይል ከጨበጡ መንበረ ስልጣናቸውን ያደላድሉና አትንኩኝ ባይ ይሆናሉ። ከስልጣን ከመነሳት ሞትን ይመርጣሉ። የስልጣን እድሜያቸውን ለማራዘም ሲሉም ህገ መንግስቱን ከማሻሻል ጀምሮ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም።

እነርሱን ከሚመስላቸው ውጭ ለሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅትም ሆነ አገርን ለመምራት አቅምም ሆነ ብቃቱ ላላቸው ግለሰቦች በማንኛውም መንገድ ቢሆን ስልጣን ለመልቀቅ ፍቃደኞች አይሆኑም። በዚህም ምክንያት ከህዝባቸው ጋር አይጥ እና ድመት ሆነው ይኖራሉ። ተቃውም ቢበረታባቸውም እንኳ ዙፋናቸውን ለማስረከብ ፈቃደኛ አይሆኑም።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የአንዳንድ አገራት ህዝቦች የማይደፈረውን በመድፈር የአንጋፋ መሪዎቻቸውን እድሜ ለማሳጠር ጠንካራ ተቃውሞ ማሰማት ጀምረዋል። በዚህ ተግባራቸውም ለመሪዎቹ የመውጫ በር ያሳዩ አገራትም ታይተዋል።

ያለፉትን ሶስት ዓመታት ብንመለከት እንኳን አንጋፋዎቹ መሪዎች በሚመሩት ህዝብ ጠንካራ ተቃውሞ ተፍረክርከው የሚወዱትን ስልጣን ሳይወዱ በግድ ለመልቀቅ ሲገደዱ አይተናል። ከእነዚህ መሪዎች ቀዳሚው የቡርኪና ፋሶው ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓውሬ ናቸው። ብሌስ ኮምፓወሬ በስልጣን ለመቆየት ህገ መንግስታቸውን ለማሻሻል ሲዳዱ በህዝባቸው መሪር ተቃውሞ ለ 27 ዓመታት ከተቀመጡበት ዙፋን እ ኤ አ በ2014 ተነስተዋል፡፡

22 ዓመታት ጋምቢያን የመሩት ያህያ ጃሜ ባሳለፍነው ዓመት በምርጫ ተሸንፈውም ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ፈቃደኝ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ይሁንና በክፍለ አህጉርና አህጉር አቀፍ ደረጃ በተደረገባቸው ጫና የሚወዱትን ስልጣን እንዲለቁ ተገደው ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ እንዲኮበልሉ ተደርገዋል። የአንጐላው ፕሬዚዳንት ሆሴ ኤድዋርዶ ዶስ ሳንቶስም እንዲሁ ለአራት አስርት ዓመታት ከተቆናጠጡበት ፕሬዚዳንታዊ ስልጣን በያዝነው ዓመት በግፊት እንካችሁ ብለዋል።።

የቅርቡን እንኳን ብንወሰድ የዚምባቤዌን አብዮት ማንሳት እንችላለን። «ከአምላክ በቀር ስልጣኔን የሚወስድ አይኖርም በሚል እስከ ህልፈተ ሞታቸው በስልጣን ለመቆየት ያስቡ የነበሩት የ93 ዓመቱ አንጋፋ መሪ ሙጋቤ፤ በወታደራዊ ሃይል በተደረገባቸው ጫና ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው አስረክበዋል።

በመሰል የህዝባቸው ጠንካራ ተቃውሞም ይሁን በምርጫ ስልጣን ያስረከቡ መሪዎች የመኖራቸውን ያህል አሁንም ለረጅም ዓመታት የተቀመጡበትን ዙፋን ማስረከብ የማይፈልጉና የመሪነት ስልጣናቸውን የሙጥኝ ብለው የተቀመጡ አንጋፋ መሪዎችም አሉ።

የኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዚዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጉዌማ እ ኤ አ ከ1979 ጀምሮ ዛሬም ድረስ በስልጣን ላይ ናቸው። የካሜሮኑ አቻቻው ፖል ቢያም ምዕራብ አፍሪካዊቷን አገር ማስተዳደር ከጀመሩ አራት አስርት ዓመታት ለመድፈን ተቃርበዋል። ሌላኛው የኮንጎ ብራዛቪል መሪ ዴኒስ ሳሱ ንጉዌሶ በመንበረ ስልጣናቸው ከተቀመጡ 33 ዓመት ተቆጥረዋል።

ከእነዚህ መሪዎች ቀጥሎ ረጅም ዓመታት በስልጣን በመቀመጥ ስማቸው ከሚጠቀሱ መሪዎች አንዱ የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ናቸው። ሙሴቬኒ እኤአ በ1986 በመፈንቅለ መግስት ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ምስራቅ አፍሪካዊቷን አገር ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት መርተዋል።ፕሬዚዳንቱ በእነዚህ ዓመታት መንበረ ስልጣናቸውን አላስደፈሩም። አገራቸው ያካሄደቻቸው አምስት ምርጫዎች ውጤትም የእሳቸውን አሸናፊነት ከማብሰር ይልቅ የተለየ ነገር ይዘው አልመጡም።

ሙሴቬኒ ስልጣን ስለመልቀቅ አስበው አያውቁም። ፍላጎቱም የላቸውም። ይልቅስ በቀጣዩ የአገራቸው ምርጫ ለስድስተኛ ጊዜ መሳተፍ ይፈልጋሉ። እርሳቸው ስልጣናቸውን ማራዘም ይፈልጉ እንጂ እንደ ቀደሙት ጊዜያት አሁን ፍላጎታቸውን በቀላሉ ማሳካት የሚሆንላቸው ግን አይመስልም። የዚህ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የአገራቸው ህገ መንግስት ነው።

የዩጋንዳ ህገ መንግሥት አንቀፅ 102 አንድ ሰው ፕሬዚዳንት ለመሆን ብቁ ነው የሚያሰኘውን የእድሜ ጣሪያ ገደብ በግልፅ አስቀምጧል። በህገ መንግሥቱ መሰረትም ማንኛውም ሰው አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት ለማስተዳደር ብቁ የሚሆነው እድሜው ከ 35 ዓመት በላይ እና ከ75 ዓመት በታች ሲሆን ብቻ ነው።

ሙሴቬኒ አሁን 73 ዓመታቸው ነው። ዩጋንዳም ቀጣዩን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እ..አ በ2021 ታካሂዳለች። ያኔ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት 76 ዓመት ይሆናቸዋል። በዚህ ስሌት ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ በስልጣን መቆየት የሚችሉት ሙሴቬኒ በቀጣዩ ምርጫ ለመወዳደር ይቸገራሉ። ይህ እንዳይሆን ከተፈለገና በምርጫው እንዲወዳደሩ ለማድረግ ታዲያ የአገሪቱን ህገ መንግሥት መለወጥ የግድ ይላል። ሙሴቪኒ ስልጣናቸውን ለማራዘም ያላቸውን ፍላጎት እውን ለማድረግ እድሜን በሚመለከት በህገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ህገ ደንብ ለማሻሻል ሲንደረደሩ ቆይተዋል።

ፕሬዚዳንቱ በዚህ ሂደት ላይ እያሉ ነበር ከወደ ሃራሬ ያልተጠበቀ የለውጥ አውሎ ነፋስ የተከሰተው። ይህ የረጅም ጊዜ የስልጣን አጋርና አቻቸውን ሮበርት ሙጋቤን ዙፋን የነቀነቀው የለውጥ አውሎ ንፋስ ታዲያ ለሙሴቬኒ ሰላም የሰጠ አይመስልም። አውሎ ንፋሱ ለሙሴቬኒ ብቻም ሳይሆን በመግቢያችን ለጠቀስናቸው ለሌሎች አንጋፋ መሪዎችም የማንቂያ ደውል ይሆናል። ከሁሉም በላይ ግን ሙሴቬኒን ያስደነገጠ ሳይሆን አልቀረም።

እንደ የሰሞኑ የሮይተርስ ዘገባ፤ በሃራሬ የተነሳው የለውጥ ነፋስ ከማንም በላይ አንጋፋዎቹን መሪዎች ያስጨንቃል። በተለይም ለካምፓላው መንግስት አስደንጋጭ የሆነ ይመስላል። የፕሬዚዳንቱ የሰሞኑ ተግባር ደግሞ ይህን እንደሚያስመሰክር ዘገባው ያትታል።

ዘገባው ፕሬዚዳንቱ «የኡጋንዳ ኢኮኖሚ እየተሻሻለ ነው፤ የአገሪቱ መንግስትም፤ ለወታደራዊ ሃይሉ ለመንግስት ሰራተኛው ለጤና ባለሙያዎች ለመምህራን የደሞዝ ማሻሻያ ያደርጋል»ሲሉ በቲውተር ገጻቸው ላይ መልዕክት ማስተላለፋቸውን በዋቢነት ይጠቅሳል።

ዘገባው እንዳመለከተው ይህ የፕሬዚዳንቱ ተግባር 37 ሚሊዮን ህዝብ በሚኖርባት አገር የተለያየ ስሜት እንዲፈጠር አድርጓል። ተግባሩን በቀናነት የተመለከቱት ጥቂቶች ሲሆኑ፣ አብዛኞቹ ፕሬዚዳንቱ ከዚህ ውሳኔ የደረሱት ስልጣናቸውን ለማቆየት ካላቸው ፍላጎት የህዝብን ድጋፍ ለማግኘት በሃራሬ የተነሳው የለውጥ አብዮት ካምፓላ እንዳይደርስ በመስጋት ነው ይላሉ።

ፐሬዚዳንቱ ለአገሪቱ ሰራተኞች ደሞዝ በማሻሻል ብቻ አለመወሰናቸውን የሚናገሩም አሉ። በሜልና ዘጋርዲያን የዜና አውታር ላይ አስተያየቷን ያሰፈረችው ኢቴል ሻኪራ «ሙሴቬኒ ደሞዝ ማሻሻያ ብቻም ሳይሆን የአንዳንድ የካቢኔ አባላት ለውጥም አድርገዋል፣ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችን የማሸጋሸግ ተግባርም ፈፅመዋል» ትላለች።

በፕሬዚዳንቱ ወገን የተሰለፉ አካላት በአንፃሩ የወታደራዊ አመራሩ ሽግሸግ የስራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁት ለመተካት የተካሄደ እንጂ ሌላ ስጋትን ተከትሎ የተፈፀመ እንዳልሆነ በማስረዳት ይሟገታሉ። ለስራተኞች የተደረገው የደሞዝ ማሻሻያም ቢሆን የአገሪቱ ኢኮኖሚ አስደማሚ የተባለ እምርታ ማስመዝገቡን ተክትሎ የተወሰደ እርምጃ መሆኑ ይታወቅ» እያሉ ናቸው፡፡

አሶሼየትድ ፕሬስ በበኩሉ ሙሴቬኒ በወታደሩ ሃይል ላይ ማተኮራቸው ታቅዶበት የተከወነ መሆኑን ያትታል። እንደ ዘገባው ከሆነ፤ ሰውየው ስልጣን የያዙት በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ነው። እናም የወታደር አቅም ምን ማለት እንደሆነ እስከ ምን እንደሚጓዝ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ከወታደራዊ ሃይሉ ድጋፍ ውጪ በስልጣን መቆየት እንደሚቸግራቸው አይጠፋቸውም።

እንደ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ፤ፕሬዚዳንቱ ምትክ የሚሉት የላቸውም። ምትክ ብለው ሲናገሩለት የሚደመጥም የለም። ምትክ ብለው ማስቀመጥ አይወዱም። ፓርቲያቸውም ቢሆን ድንገተኛ ለውጥ ቢመጣና አፋጣኝ ምትክ ቢፈለግ እንኳ ከመዋከብ ይልቅ አፋጣኝ መልስ የመስጠት አቅም ሆነ አደረጃጃት የለውም።

ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር በሙሴቬኒ የስልጣን ዘመን ይህ ነው የሚባል የተጋነነ ተቃውሞና ሁከት ደርሶባት አያውቅም። ይሁንና አሁን ነገሮች እየተለወጡ ነው። በተለይ የፕሬዚዳንቱን የስልጣን እድሜ ገደብ ለማንሳት የተደረገው ሂደት ብዙዎችን አስኮርፏል። እናም በአገሪቱ ህዝብ ተቃውሞና ነውጥ መታየት የጸጥታ አካላትም አፀፋውን መመለስ ጀምረዋል።

በሃራሬ የተነሳው የለውጥ አውሎ ንፋስ ከኡጋንዳ ተሻግሮ በሌሎች አገራት አንጋፋ መሪዎች ላይ ጭንቀት ማሳደርም ጀምሯል። አንጋፋዎቹ ስልጣን ወዳድ መሪዎች በሚያስተዳድሯቸው አገራት የሚኖሩ ህዝቦችና የተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንፃሩ የልብ ልብ አግኝተዋል። እናም የአንጎላና የዙምባብዌን አንጋፋ መሪዎች የተካው አይነት የለውጥ አብዮት ወደ ሌሎች አፍሪካ አገራትም እንደሚደርስ አትጠራጠሩ የሚሉ ተበራክተዋል።

አገራቸውን ማስተዳደር ከጀመሩ አራት አስርት ዓመታት ያስቆጠሩት የካሜሩኑ ፖል ቢያ ደግሞ ይህ ስጋት ከተደቀነባቸው አገራት መሪዎች አንዱ ናቸው። የካሜሮን ህዝብ ፓርቲ ዋና ፀሃፊ ፍራንኪ ኢሲ እንደሚገልፀው፤መሪዎች ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ የስልጣን ርክክብ በማድረግ ምትክ እንዲያገኙ መወሰን ይኖርባቸዋል፤ይህ ካልሆነ የተወሰነ ጊዜያትን ቢወስድም በስተመጨረሻ የአገራቸው ህዝብ ራሱ የመውጫ መንገድ ያሳያቸዋል» ሲል ተደምጧል።

የቶጎ ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ ብርጊቲ አጃማድቡ ጆንሰን በሃራሬ የተነሳው የለውጥ አውሎ ንፋስ ቶጎ ሎሜ እንዲደርስ ፍላጎት አለው። ሰላማዊ በሆነ መንገድ ስልጣንን የማስተላለፍ ሂደት በዙምባብዌ ህዝብ ዘንድ ደስታ እንደፈጠረ ሁሉ ቶጎአዊያንም በመዲናቸው ዋና ዋና ጎዳናዎች ደስታቸውን ሲገልፁ መመልከት ይፈልጋል።ይህ እንደሚሆንም ተስፋ አለው።

 

ታምራት ተስፋዬ

 

 

Published in ዓለም አቀፍ

 

ግንባታው ላለፉት 20 ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች የተጓተተው የፍል ውሃ ፕሮጀክት በሚል የሚጠራው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ያስጀመረው ህንጻ ግንባታ በሦስት ምዕራፍ ተከፍሎ እንደሚካሄድ ማህበሩ ገለጸ፡፡ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር አህመድ ረጃ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ማህበሩ ከመንግሥት በነጻ ባገኘው ቦታ ያስጀመረው የህንጻ ግንባታ የዘገየው በዲዛይን ለውጥና የመጀመሪያ ክፍያ ተቀብሎ ወደ ሥራ የገባው የመጀመሪያው ተቋራጭ በገባው ውል መሰረት ግንባታውን ባለማከናወኑና የፍርድ ቤት ክርክር በመጀመሩ ነው። የግንባታው መጓተት ማህበሩ እንደሚያገኝ ይጠብቅ የነበረውን ገቢ አሳጥቶታል።

የፍርድ ቤት ክርክሩ በግልግል ዳኝነት ለማህበሩ መወሰኑንና አፈጻጸም ላይ የተፈጠረው መዘግየት ሌላው ችግር እንደነበር የገለጹት ዶክተር አህመድ፣ ተቋራጩ ያስቀመጣቸውን አንዳንድ ማሽነሪዎች በመያዝ ወደ ከተማ አስተዳደሩ በሚኬድበት ወቅት ደግሞ ለቦታው የሚመጥነው 16 ወለል ያለው ህንጻ አይደለም በመባሉ ወደ ዲዛይን ክለሳ መገባቱንም አስታውቀዋል።

ማህበሩ ሌላ ዲዛይን በማሰራትና አዲስ ካርታ በማውጣትም ከሚድሮክ ኢትዮጵያ ጋር የ213 ሚሊዮን ብር ውል ተፈራርሞ ሁለት ባለ 21 ወለል ህንጻዎች እንዲሁም አንድ ባለ አራት ወለል የመኪና ማቆሚያ ያለውና አራት ወለል ህንጻ ደረጃ በደረጃ ለማከናወን ማቀዱን ገልጸዋል ።

ግንባታው ከፍተኛ የሆነ መዋዕለ ንዋይን እንደሚጠይቅ ዶክተር አህመድ አብራርተው፣ ሥራው በሦስት ምዕራፎች እንዲከናወን መወሰኑን ተናግረዋል።የመጀመሪያው ምዕራፍ ማለትም ከወለል በታች 4 ፎቅ መኪና ማቆሚያና ከወለል በላይ 4 ፎቅ እየተገነባ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

ዶክተር አህመድ ፕሮጀክቱ በእቅዱ መሰረት ከተሳካ ማህበሩ አስተማማኝ የገቢ ምንጭ እንደሚኖረው ጠቅሰው፣ የፌዴራል መንግሥት፣ የክልል መንግሥታት፣ ህብረተሰቡ እንዲሁም የማህበሩ አባላት በሚዘጋጁ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች ላይ የላቀ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፍልውሃ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ግዛው አሰፋ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የመጀመሪያውን ምዕራፍ ለመገንባት የአካባቢውን ልል አፈር የመሙላትና የመጠቅጠቅ ሥራ ተከናውኖ መሬቱ ህንጻውን የመሸከም አቅሙ ተፈትሾ 95 በመቶ ውጤት መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ኮለኖቹን የማቆም ሥራ እንደሚጀመርም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም የሥራው 9ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን ገልጸው፣ የሚድሮክ ኢትዮጵያ የሥራ ተቋራጭ ለሥራው የሚያስፈልጉትን መሳሪያዎችና የሰው ሀይል አሟልቶ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ የመጀመሪያ ምዕራፍ የህንጻ ግንባታ ቢበዛ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ እንደሚገባም አስረድተዋል።

እንደ ፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ማብራሪያ፤ህንጻው የሚያርፍበትን ሥፍራ በሙሉ በንጣፍ መሰረት የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፣ አካባቢው ወንዝ የሚያልፍበት እንደመሆኑ መጠን ይዞታውን በኮንክሪት በመሙላት የውሃ ስርገትን የመከላከል ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

ህንጻዎቹ ለመኖሪያና ለቢሮ እንዲሁም ለተለያዩ የንግድ ሥራዎች እንደሚከራዩ እና በአካባቢ ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይፈጥሩ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጎ እንደሚገነቡም ለማወቅ ተችሏል።

 

እፀገነት አክሊሉ

 

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።