Items filtered by date: Wednesday, 06 December 2017

አቶ ዘነበ ተሰማ፤

 

ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማዘውተር ጥሩ የመዝናኛ ምንጭ ነው። ከመዝናኛነቱ ባሻገር በሽታ የመከላከል አቅምን በማጠናከር ረገድ ያለውን ሚና ተራማጅ እንደሆነ ይነገራል። ሌላው ዘርፍ ከሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች በአገር ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት ያለው ፋይዳ ተጠቃሽ መሆኑን የዘርፍ ምሁራን ይናገራሉ። በአጠቃላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አምራችና ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር እገዛው ከፍተኛ እንደሆነ ያመላክታሉ።

የዘርፍን ተሻጋሪ ፋይዳ ተረድቶ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በአፍሪካ ያለው ልምድ ከሌላው ዓለም አንፃር ዝቅተኛ ስፍራ እንደሚይዝ መረጃዎች ያመለክታሉ። በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታም ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን አብሮ የሚነሳ ጉዳይ ነው። ስፖርቱን ልምድ የማድረግ ባህል አነስተኛ ነው፡፡ ልምዱን ተደራሽ ለማድረግ ጥረቶች ቢደረጉም በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ቅቡልነት እምብዛም ሆኖ ይስተዋላል። እንቅስቃሴውን ለማድረግ ቢጣርም በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዳልሆነ ባለሙያዎች ያብራራሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስፖርት ለሁሉም ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ ዘነበ ተሰማ፤ በአገሪቱም ሆነ በአዲስ አበባ የስፖርት እንቅስቃሴ የማድረጉ ልማድ እምብዛም ነው። ይህን ሁኔታ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ዕድሜው ትንሽ ቢሆንም «ስፖርት ለሁሉ» የውድድር መድረክ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ።

ፕሬዚዳንቱ፤ እንደሚያብራሩት በስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማሳተፍ የስፖርቱን ደረጃ ከፍ ለማድረግ እና የዜጎችን ምርታማነት ለማረጋገጥ የጎላ ሚና አለው፡፡ ስፖርት ለሁሉም ይሄንኑ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ከስምንት ዓመት በፊት በሁሉም የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ሰዎች ለማዳረስ በሚል ሃሳብ ተቋቁሟል። የተቋቋመው ኮሚቴ ውድድሮችን ሲያዘጋጅ ቆይቷል።

ህብረተሰብ በሚኖርበት፣ በሚሠራበት፣ በሚማርበት፣ በሚያስተምርበት ቦታ ሁሉ የአካል እንቅስቃሴ በማድረግ ጤናውን እንዲጠብቅ ያደርጋል። ይህንኑ መሰረት በማድረግም የሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ሁለት ዓላማዎችን አንግበዋል። አንደኛው እያንዳንዱ ዜጋ ጤንነቱን በስፖርት እንዲጠብቅና እራሱን ከተለያዩ በሽታዎች እንዲታደግ ማስቻል ነው። ሁለተኛው የአንዱ ተቋም ከሌሎች ተቋም ሠራተኞች የልምድ ልውውጥ በማድረግ የተቀላጠፈና መልካም ግንኙነት ያለበት የሥራ ቦታን መፍጠር የስፖርት ለሁሉም ሌላው ዓላማ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ይናገራሉ።

የስፖርት ለሁሉም ያለፉት ሰባት

ዓመታት ጉዞ

አቶ ዘነበ፤ የስፖርት ለሁሉም ማህበረሰብ የስፖርት ተሳትፎውን በማጠናከር ረገድ ሚናውን በመወጣት አንድ ዕርምጃ ተራምዷል። ቅንጅታዊ አሠራርን በማጎልበት ረገድ ለውጦች አሉ። በተለይም በአነስተኛ ደረጃ የተቀመጠውን የስፖርታዊ እንቅስቃሴ ልምድን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚደርስበትን አጋጣሚ ለመፍጠር እንደመንደርደሪያ የሆነ ውጤት ታይቷል። ለዚህም በማሳያነት ስፖርት ለሁሉም ሲጠነሰስ አስር ያህል ተሳታፊ ቡድኖች ብቻ በመያዘ ሲሆን፤ አሁን ከ60 በላይ ተቋማት ከ99 በላይ ቡድኖች በውድድሩ ተሳታፊ ናቸው። ነገር ግን አሁንም የከተማው ህብረተሰብ በስፖርት ልማትና ተሳትፎ ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ለማለት እንደማያስደፍር ተናግረዋል።

«ባለፉት ሰባት ዓመታት አነስተኛ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ልምድን ስፖርት ለሁሉም ባከናወናቸው ውድድሮቹ ማነቃቃት ተችሏል። በነበረው የውድድር ጉዞ የጤና ተቋማት፣ አርቲስቶች፣ መገናኛ ብዙሃን፤ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች ተቃማት ተሳታፊ ነበሩ። ይህ እንቅስቃሴ ቀጣይነት እንደሚኖረውም አብራርተዋል።

የስፖርተኛው ቁጥር እየጨመረ ቢሆንም በአዲስ አበባ ከሚኖረው የሰው ብዛት አንጻር ለውጡ ዘገምተኛ ነው። የኮሚቴው ፍላጎት እያንዳንዱ ተቋም እና በአስሩም ክፍለ ከተሞች የሚኖረው የህብረተሰብ ክፍል ማሳተፍ ቢሆንም ካለው የበጀት ችግር አኳያ በታሰበው ደረጃ መሄድ አልተቻለም። በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍ ተሳታፊዎች የእራሳቸውን ወጪ በእራሳቸው አቅም እንዲሸፍኑ በማድረግ እና አጋር ድርጅቶችን በማፈላለግ ከችግሩ ለመውጣት እየተሞከረ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ይገልጻሉ።

የተሳትፎ ጉዳይ እንደ ጉድለት

የስፖርት ለሁሉም ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ ዘነበ፤ ከዚህ በተጓዳኝ የተሳታፊውን ቁጥር ለማብዛት የተሠራውንና በቀጣይነት የሚሠሩትን ሥራዎች መኖራቸውንም ያነሳሉ። በክፍለ ከተማ እና በወረዳ ደረጃ በመውረድ ነዋሪዎች የእራሳቸውን ቡድን ማሳተፍ በሚፈልጉት የስፖርት ዓይነት ተሳታፊ እንዲያደርጉ እስከ መቀስቀስ ተሠርቷል። ከዚሁ ጎን ለጎን አሠልጣኞችን በመቅጠር ህብረተሰቡ በአካባቢው በቀላሉ እና በነፃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ስልጠና እንዲያገኙ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራዎች ተሠርተዋል።

በስፖርት ለሁሉም እቅድ ውስጥ ተካትተው ከሚሠሩ ተግባራት መካከል በዋናነት ትኩረት የተሰጠው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ነው። ማህበረሰቡ ከስፖርት ሳይገለል በሚኖርበት፣ በሚማርበትና በሚሠራበት አካባቢ ተገቢ የሆኑ የስፖርት ዓይነቶችን በመሥራት ጥረት ማድረግ እንዲችል ግንዛቤ ተሰጥቷል፡፡ በከተማዋ በሚገኙ አስር ክፍለ ከተሞች በተዋቀሩ ኮሚቴዎች አማካኝነት ሥራው ተደራሽ በማድረግ ስኬታማ ሥራ እንደሚሠሩ አብራርተዋል።

የስምንተኛው የውድድር ምዕራፍ ቅድመ ዝግጅት

«ስፖርት ለሁሉም ዘንድሮ ለስምንተኛ ጊዜ ቀጥሎ ይካሄዳል» ያሉት አቶ ዘነበ ውድድሩን በተለየ እና በተሻለ ደረጃ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ እንገኛለን። ከዚህ በፊት የነበሩትን ተሳታፊ ተቋማትንም ሆነ አካላት ቁጥር ለማብዛት የተሠሩ ሥራዎች በመኖራቸው የዘንድሮው «ስፖርት ለሁሉም» ውድድር ተሳታፊ ተቋማትም ሆኑ ቡድኖች ቁጥር ከባለፉት ውድድሮች ያሻቅባል ተብሎ እንደሚጠበቅ እምነታቸውን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት በነበረው ውድድር ያጋጠመውን ችግር ከመቅረፍ አኳያም ዝግጅት ተደርጓል። ባለፈው ውድድር በቂ የማወዳደሪያ ስፍራ አለመኖር አንዱ ችግር ነበር፡፡ በወቅቱም ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ችግሩን ለመቅረፍ የትምህርት ቤቶችንና የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ሜዳዎችን በማስፈቀድ ውድድሮች ሳይስተጓጎሉ እንዲካሄዱ ለማድረግ ችሏል፡፡ ይህ ችግር በስምንተኛው ስፖርት ለሁሉም ውድድር ላይ እንዳይደገም ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል። ዝግ የነበሩት የስፖርት ሜዳዎች ዘንድሮ ክፍት እንዲሆኑ ተደርገዋል ብለዋል።

የሴቶች ተሳትፎ መጨመር

አቶ ዘነበ ስፖርቱን ተደራሽ በማድረግ ሂደት የሴቶች ተሳትፎ አነስተኛ ነው። በተቻለን መጠን የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ተሳታፊ ተቋማት ሴቶችን እንዲያነሳሱ እና እንዲያበረታቱ በማድረግ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ከነበረው ተሳትፎ በላቀ ሁኔታ የሴቶች ተሳትፎ ይኖራል። በውድድሩ የሚሳተፉ ተቋማትም ሆኑ ቡድኖች ገና እየተመዘገቡ በመሆኑ አሁን ላይ ይህን ያህል ተሳታፊ ይኖራል የሚለውን ለማስቀመጥ አዳጋች ነው። አጠቃላይ ምዝገባው እስከ ታኅሣሥ 30 ይጠናቀቃል የሚል ግምት አለ። በዚያን ወቅት የተሳታፊውን ቁጥርም ሆነ የውድድሩን መጀመሪያ ቀን እናሳውቃለን ብለዋል።

 

ዳንኤል ዘነበ

 

 

Published in ስፖርት

በኬንያ አስተናጋጅነት በመካሄድ ላይ የሚገኘው 39ኛው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ካውንስል (ሴካፋ) ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመጀመሪያ ጨዋታው ድል ቀንቶታል። ከደቡብ ሱዳን ጋር ጨዋታውን ያደረገው ብሄራዊ ቡድኑ 30 በሆነ ውጤት ነው ያሸነፈው።

ከህዳር 24 ጀምሮ በጎረቤት አገር ለሚካሄደው የሴካፋ ዋንጫ፤ አስር አገራት (ሁለት ተጋባዠ እና ሰባት የሴካፋ ዞን አባል አገራት) ተካፋይ እየሆኑበት ይገኛል። አገራቱ በሁለት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ምድብ አዘጋጇ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሊቢያ፣ ታንዛኒያ እንዲሁም ዛንዚባር ተደልድለዋል። በሁለተኛው ምድብ ደግሞ ዩጋንዳ፣ ዚምባብዌ፣ ብሩንዲ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ይገኛሉ።

በአዘጋጇ ኬንያ እና ሩዋንዳ መካከል የተካሄደው የመክፈቻ ጨዋታም በኬንያ የ20 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ፤ ኬንያ የምድቡ መሪ ሆናለች። ያለ ምንም ግብ የተለያዩት ተጋባዧ ሊቢያ እና ታንዛኒያ ደግሞ አንድ አንድ ነጥብ በመያዝ እኩል ሆነዋል። በምድብ ሁለት በተካሄደ ጨዋታ የተገናኙት ዩጋንዳ እና ብሩንዲም ጎል ሳያስቆጥሩ ነበር የተለያዩት።

በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመሩት ዋልያዎቹ 22 ተጫዋቾችን በመያዝ ወደ ኬንያ መጓዙ የሚታወስ ነው። በምድብ ሁለት የሚገኘው ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታውን ትናንት በካካሜጋ በሚገኘው ቡኩንጉ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ከደቡብ ሱዳን ጋር አድርጓል። በጨዋታውም ዋልያዎቹ ደቡብ ሱዳንን በሰፊ የጎል ልዩነት አሸንፈዋል። አቤል ያለው በ24ኛውና በ50ኛው ደቂቃ ግቦቹን ሲያስቆጥር፤ አቡበከር ሳኒ ደግሞ ከሰባት ደቂቃ ሦስተኛውን ግብ ከመረብ አገናኝቷል።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከጨዋታው በፊት፤ ቡድኑ ለጨዋታ ያለው ስሜት እና ተነሳሽነት መልካም የሚባል እንደሆነ መግለፃቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አስነብቧል። ጨዋታው ቀላል እንደማይሆን ይገመታል፤ ምክንያቱም የደቡብ ሱዳን ቡድን አዲስ ጉልበት ይዞ የሚመጣ ቡድን ነው ማለታቸውንም ድረገፁ ጨምሮ ዘግቧል። ደቡብ ሱዳን ፊፋ ባወጣው የአገራት የእግር ኳስ የደረጃ ሰንጠረዥ 152ኛ ላይ ስትገኝ፤ ኢትዮጵያ ደግሞ 145ኛ ላይ ተቀምጣለች።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሴካፋ ዋንጫ ተሳትፎው አራት ዋንጫዎችን ማንሳቱ ይታወቃል። በ2009.ም በአዲስ አበባ አዘጋጅነት በተካሄደው የሴካፋ ዋንጫ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።

 

ብርሃን ፈይሳ

Published in ስፖርት
Wednesday, 06 December 2017 18:31

ክብር ለደግነት

 

በዕድሜ ዘመናቸው ለአገራቸውና ለህዝባቸው የሚችሉትን ሁሉ አድርገውና አበርክተው የአረጋዊነት ዘመን ላይ ሲደርሱ ሁሉም ጧሪ ቀባሪ ያገኛሉ ማለት አይቻልም። በዚህም ምክንያት ብዙዎች ጎዳና ላይ መውደቅ የሰው እጅ አይቶ መኖር እጣ ፋንታቸው ይሆናል። በኢኮኖሚ በበለጸጉ አገራት እነዚህን የአገር ባለውለታዎች መንግስት እስከ መጨረሻው የዚህ ምድር ቆይታቸው ድረስ ይጦራቸዋል። እንደ እኛ ባሉ አገራት ደግሞ የመንግስተ እጅ ሲያጥር ግለሰቦች ያንን ሃላፊነት ሲወጡ ይታያል። የአዲስ ዘመኗ መልካምስራ አፈወርቅም በመቄዶንያ እየተደረገ ያለውን እገዛና የአረጋዊያኑን ህይወት እንዲህ ትነግረናለች።

 

ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው በትምህርት የጎለበተው ማንነታቸው አቅማቸውን ሳይሰስቱ ለወገን የሚተርፍ አኩሪ ተግባርን እንዲከውኑ አስችሏቸዋል።ጊዚያቸውን በሙሉ ለስራና ለትምህርት መስጠታቸውም የግል ህይወታቸውን ቦታ ማጣበቡን ያውቁታል። ይህ ሀሳብ ግን ከያዙት ዓላማ እንዲያዘናጋቸው አይሹም ነበር።

ዛሬ ላይ ሆነው የትላንቱን ማንነታቸውን ሲያስቡት ከማይረሳ ትዝታ ውስጥ ይገባሉ።ህይወት በብዙ ብትፈትናቸውም ያለፉበትን አስቸጋሪ መንገድ ግን አማረውት አያውቁም። ዕድሜያቸው ቢገፋም ዛሬም የተለየ ብርታትና ጥንካሬ አብሯቸው ነው። አሁንም ቢሆን ከሳቸው የሚጠበቀውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ናቸው። አቶ ተከስተ ብርሀን መንክር።

ከዛሬ 45 አመታት በፊት በመምህርነት ሙያ ከተቀጠሩ ብርቱና ጎበዝ ምሁራን መሀል አንዱ ናቸው። በቀለም ትምህርት ዘልቀዋል የተባሉ በጣት በሚቆጠሩበት ዘመንም እሳቸው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመያዝ ችለው ነበር። ሁሌም መስራትና መማርን ልምድ ያደረጉት ጠንካራው ምሁር በወቅቱ ሚስት ማግባትና ልጆች ማፍራት እንዳለባቸው አላጡትም። ይህ ሀሳብ ግን ከያዙት መንገድ የሚያደናቅፍ ቢመስላቸው ቅድሚያውን ሁሉ ለትምህርትና ለተቀጠሩበት ሙያ ሰጥተው ዕድሜያቸውን በብቸኝነት ሊገፉ ግድ ሆነ።

አቶ ተከስተ በጀርመን ሀገር ለትምህርት በቆዩበት ጊዜ የተሻለ ልምድና ዕውቀትን አትርፈዋል።ይህ እውነታም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በመምህርነት እንዲሰሩ አስችሏቸዋል። አመታትን በሚወዱት ስራ ላይ ቆይተው በጡረታ ሲገለሉም እንደአብዛኞቹ እረፍትን አልፈለጉም። በዕውቀት የዳበረው አዕምሯቸውን ሊጠቀሙበት በመሻት ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆነው የግል ኢንቨስትመንቱን ፈጥነው ተቀላቀሉ።

ምሁሩ ተከስተ መምህርነትን ተሰናብተው ወደ ግል ስራ ሲገቡ አብረዋቸው ካሉ አጋሮቻቸው ጋር ግዴታቸውን ሊወጡ ግድ ነበር። ይህ ጥረትና ልፋት ግን እንዳሰቡት ሆኖ ፍሬ አላስገኘላቸውም። ሩቅ አሳቢው ተከስተ ይህ መሆኑ ሰላም ቢነሳቸው ብስጭትና እልህ አብሯቸው ውሎ አደረ። የዚህ ውጤት ደግሞ ጤና ነስቶ ከቤት ያውላቸው ጀመር። 31 አመታትን ከስኳር ህመም ጋር አብረው ቆይተዋል። እነዚህን ጊዚያት በጥንቃቄ ማሳለፋቸው ግን በሽታው ለከፋ ጉዳት ሳያጋልጣቸው እንዲቆይ አድርጓል።

አንድ ቀን ግን ሲመላለስባቸው የነበረው ህመም ክፉኛ ጸናባቸው። ውስጣቸው የቆየው ንዴትና ብስጭትም በሽታቸውን አባብሶ ከሆስፒታል ደጃፍ አደረሳቸው። ሁኔታቸውን የተረዱ ሀኪሞች ተሯሩጠው ሊረዷቸው ፈጠኑ። በዕለቱ የተደረገላቸው እርዳታ ነፍሳቸውን ከሞት ታደገው። የስኳር ህመሙ ከአቅም በላይ መጨመር ግን አንድ እግራቸውን ከመቆረጥ አላዳነውም።

ይህ ከሆነ በኋላ ጠንካራው ተከስተ ቤት ሊውሉ ግድ ሆነ። ከሁሉም በላይ ግን ብቸኝነት ችግራቸውን አባሰው። በቅርብ ተገኝቶ ህመማቸውን የሚጋራ የቅርብ ቤተሰብ ያለመኖሩም ሌላ መከራ ይሆናቸው ጀመር። ጠያቂ ዘመድ፣ አስታማሚ ሚስትና ልጆች የላቸውምና ጧት ማታ የጠያቂዎችን እጅ ናፈቁ። ባዶ ቤት ውሎ ማደርና የሰዎችን እጅ ማየቱም ብርቱውን ምሁር ሆድ አስባሳቸው።

ከጊዚያት በኋላ ከማዘር ትሬዛ በጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ለእንክብካቤ መግባታቸው መፍትሄ ሆኖ አገዛቸው። ይህ መሆኑ ለአንዳንዶች ቢያስገርምም ለብቸኛው ታማሚ ግን ትልቅ እፎይታ ሆነ። ተከስተ ያለፉበትን የህይወት መንገድ ቢያውቁትም ሁሉንም እንደ አመጣጡ ተቀብሎ «ተመስገን» ማለትን አልዘነጉም። እዛም ቢሆን ያላቸውን ዕውቀትና ችሎታ ለመለገስ ወደ ኋላ አላሉም። ድርጅቱን ሊጎበኙ የሚመጡ የውጭ ዜጎችን ከሰራተኞች ጋር በማግባባትና የትርጉም አገልግሎትን በመስጠት የአቅማቸውን ሲያበረክቱ ቆዩ።

በወቅቱ ስለማንነታቸው የሰሙ አንዳንድ ሰዎች ወደሳቸው ቀርበው ከልምዳቸው ይካፈላሉ። ሁሌም ዕውቀታቸውን ለማጋራት የማይሰስቱት መምህርም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሌሎችን ለመርዳት ይበረታሉ። ከቀናት በአንዱ ቀን ደግሞ ስለሳቸው የሰሙ ሰዎች ቀርበው አነጋገሯቸው። ካሉበት ስፍራ ወጥተው እነሱ ወዳሰቡላቸው ቦታ ቢሄዱም የተሻለ መሆኑን አማከሯችው። ተከስተ ይህን ሲሰሙ የተባሉትን ለማድረግ ፈቀዱ። ከጊዚያት በኋላም የሜቄዶኒያን የበጎ አድራጎት ድርጅትን ተቀላቀሉ።

ዛሬ አቶ ተከስተ ብርሀን በሜቄዶኒያን አረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ውስጥ አመታትን አስቆጥረዋል። በስኳር ህመም ጉዳት የደረሰበት አንድ እግራቸውም ሰው ሰራሽ አካል ተገጥሞለት እንደበፊቱ ይራመዳሉ። በድርጅቱ ውስጥም የአረጋውያን ጉዳይ አስፈጻሚና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው ያገለግላሉ። አሁን እንደቀድሞው ጥንካሬና የተለየ ብርታት ከፊታቸው ይነበባል።

ዛሬ የትላንቱን ማንነታቸውን እያስታወሱ ማዘንና መቆዘም ልምዳቸው አይደለም። እንደሳቸው ዕምነት በህይወት አጋጣሚ መፈተን መልካም የሚባል ነው። ሁሉን አልፎ ለለአሸናፊነት መብቃት ደግሞ ለሌሎች ጭምር ታላቅ ተስፋ ይሆናል። ከምንም በላይ ግን በዕድሜ የገፉና የአዕምሮ ሀሙማንን በአቅማቸው መርዳታቸው ያስደስታቸዋል። ይህ አጋጣሚም ቀሪውን ህይወታቸውን ለበጎነት እንዲያውሉት ምክንያት ሆኗልና ለውስጣቸው የተረፈው ሀሴት የተለየ መሆኑን አዛውንቱ ተከስተ በኩራት ይናገራሉ።

አቶ ተሾመ ወርቁ በሜቄዶንያ መርጃ ማዕከል የመገኘታቸው ምክንያት ያጋጠሟቸው ተደራራቢ የህይወት ፈተናዎች እንደሆኑ ይናገራሉ። ከአመታት በፊት ለእስር የተዳረጉበት አጋጣሚ ቆይቶ ነጻ ቢያወጣቸውም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመለያየት ግን ሰበብ ነበር። ይህ እውነታም ቀሪውን ጊዚያቸውን በብቸኝነት እንዲገፉ ማስገደዱ አይቀሬ ሆኗል።

አቶ ተሾመ ለረጅም አመታት ያገለገሉበት መስሪያቤት ሲፈርስ ለራሴ የሚሉት ጥሪት አልነበራቸውም። ከእስር ከተፈቱ በኋላም የቤተሰቦቻቸው መበታተን ለከፋ ችግር ዳርጎ ሲያንገላታቸው ቆይቷል። ጤና በነበሩ ጊዜ ራቅ ወዳለ አካባቢ ተጉዘው ለመስራት ሞክረዋል። ውሎ አድሮ በአይናቸው ላይ የደረሰው ህመም ግን እንዳሻቸው እንዳይሆኑ እንቅፋት ፈጠረባቸው።

አስቀድሞ በአንደኛው አይናቸው ላይ የነበረ ጉዳት ቆይቶ ወደ ሌላው አይናቸው ተዛመተ። ይህም የጤንነታቸው ጉዳይ አሳሳቢ አደረገው። ይባስ ብሎ ብርሀናቸው ጨለመና አይኖቻቸው ታወሩ። ይሄኔ ተሾመ እጅግ ግራ ገባቸው። የሚመራ ልጅ የሚሰበስብ ቤተሰብ የላቸውምና በጭንቀት ተዋጡ። የዛኔ ተለይተዋቸው በነበረ ጊዜ ሚስት ለስደት ልጆችም ለመበታተን ተዳርገዋል። በመሀላቸው የነበረው የአመታት ክፍተትም ከልጆቻቸው ጋር ዳግም ሊያግባባቸው አልቻለም።

የትላንቱ ታታሪ የአሁኑ አይነስውር ጎልማሳ አሁን የሰዎችን እጅ ሊያዩ ግድ ሆነ ። በየቀኑ የሌሎችን እገዛ መናፈቃቸውም ከተረጂነት ላይ ጣላቸው። ተከራይተው ለሚኖሩበት ጠባብ ቤት ኪራይና የዕለት ቀለብ ከሚያውቋቸው እየለመኑ ማሟላት ግድ ሆነባቸው። ይህ ብቻውን ግን መፍትሄ ሆኖ አላዘለቃቸውም። ርቆ ለመሄድና ተንቀሳቅሶ ለመስራት ችግር ቢሆንባቸው አንድ ቀን ሲያስቡት የከረሙትን ሊፈጽሙ ከቤት ርቀው ዋሉ።

ወደ ሜቄዶኒያ የአዕምሮና የአረጋውያን መርጃ ማዕከል ሲደርሱ ማንነታቸውን ያዩ በጎ ሰዎች አቅፈው ተቀበሏቸው። ችግራቸውን ከስር መሰረቱ ሲያስረዱም መስሚያ ጆሮዎችን አላጡም። በዕለቱ ተቀባዮቻቸው በቀጠሮ ሲሸኟቸውና ወደመጡበት ሲመለሱ ግን አሉበት ደርሰው ይጎበኙኛል የሚል ዕምነት አልነበራቸውም።

አሁን አቶ ተሾመ በማዕከሉ አምስት አመታትን በኑሮ አሳልፈዋል። ምንም እንኳን አይኖቻቸው ከብርሀን ጋር ቢራራቁም በተለያዩ ሙያዎች ቆይተዋልና የአቅማቸውን ለማበርከት አልተቸገሩም። ህይወት በተለያየ አጋጣሚ ፈትና እዚህ ብታደርሳቸውም በማዕከሉ የሚገኙና በአዕምሮ ህመም ያሉ ሌሎችን ሲመለከቱ ከእሳቸው የሚጠበቀውን ለማድረግ ወደ ኋላ ብለው አያውቁም።

ምንግዜም ሰዎች መልካም ለመስራት ካሰቡ ሁኔታዎች ምክንያት እንደማይሆኗቸው ያምናሉ። ለዚህም ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው የሚለው አባባል ይገዛቸዋል። በማዕከሉ ያለው እውነታም ይሄው ነው። ሰዎችን ከወደቁበትና ከተረሱበት አውጥቶ ዳግም ህይወት የሚዘራበት አለም። እሳቸውንም ለዚህ ላበቃቸው የድርጅቱ መስራች ወጣት ክቡር ዶክተር ቢኒያም.. ያላቸው ምስጋና ከልብ የመነጨ ነው።

ሁለቱን የሀገር ባለውታዎች ያገኘኋቸው በቅርቡ በዋቢሸበሌ ሆቴል ጋርደን አዳራሽ ተከፍቶ በነበረውና «ክብር ለደግነት» በሚል በተሰየመው የኤን ጂኦ እና ቻሪቲ ኤክስፖ መክፈቻ ላይ ነበር።የሜቄዶኒያ መርጃ ማዕከልን ጨምሮ በርካቶች የተሳተፉበት ይህ የሶስት ቀናት ኤክስፖ የበጎ አድራጎት ተቋማት ለአገራችን፣ለአህጉራችንና ለዓለማችን እያደረጉ ያለውን በጎነት ለማመልከት ሲባል የተዘጋጀ ነው።

የኤክስፖው አዘጋጅ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ዳዊት ወልደገሪማ እንደሚሉትም የኤክስፖው መዘጋጀት ዋንኛ ዓላማ በጎ የሚሰሩ ድርጅቶችን መልካምነት ለማሳየትና የእነሱን መርህ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚቻልበትን አቅጣጫ ጭምር ለማመላከት ነው። ለወገን ደራሽነታቸውን በተግባር ያሳዩ ወገኖችን ምግባር ለማስመስከር የኤክስፖው ገጽታ አንድ ማሳያ መሆኑን በመጥቀስም በክብር ለደግነት ኤክስፖ ላይ ከስልሳ ያላነሱ ተቋማት ተሳትፈዋል ብለዋል።

 

 

Published in ማህበራዊ
Wednesday, 06 December 2017 18:25

ደብዳቤው 3

 

ይድረስ ለተከበርከው ለታፈስከው… ማነው ለታፈርከው ወዳጄ አያ ሻረው፡፡ የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ጣጣ በቅጡ እንኳ ሰላምታ እንዳላቀረብልህ አረገኝ፡፡ የዚህ አገር ምንገድ አያልቅምና እንደ ጉንዳን በየኸድኩበት ስሰለፍ እናእጁን መዋጥ አስመስሎ እየተጋፋ ከሚበረብር ወሮ በላ ኪሴን ስከላከል እውልለሀለሁ፡፡ ደሞ እኮ የተሰለፍኩትን ያህል በሰዓቱ ኸፈለግሁበት ብደርስ ምን አለበት?

እየውልህ እዚህ አገር መሂናውን የሚነዳው የትራፈሪክ ባርኔጣው ሳይሆን አይቀርም፡፡ አዳሜ መዘወሪያ ፍቃዱን ሲያዎጣ ‹‹ከራስ በላይ ነፋስ›› ብለው ያስረገሙት… ማነው ያስመረቁት ይመስል የትራፈሪክ መብራት መሀል ያንዱ መኂና ባንዱ ምንገድ ላይ ይሸነቆርልህና እርስ በርስ ጡሩምባውን እየነፋ ማለፍ የለ ማሳለፍ ዝም ብሎ መፋጠጥ ብቻ፡፡ በዚህ መሀል ሰርቶ አደር እኔ ቢጤ ምንገዱን ወይ እግዚሀር መጥቶ አያስለቅቅ ወይ ኸታክሲው ወርደን በእግራችን አንወዘወዝ… የስራው ሰዓት አለፈ-አላለፈ ስንንቦጀጀቦጅ አንድ ባለ ነጭ ባርኔጣ ይመጣና ይገላግለናል፡፡

በክብር እለፍ ላሳልፍህ ተባብሎ መዘወር የተሳነው ዘዋሪ ሁላ ባርኔጣውን ሲያይ ጥንቁቅ የስነ ምግባርና ትህትና ባለሟል፤ ተርብ የህጉ ተቆርቋሪ ሆኖ መዘወር ይጀምራል፡፡ ያው እኔና የኔ ብጤ ወደ ስራችን አረፋፍደን መግባት አለቆቻችንም ከደመዎዛችን ላይ መቆንደድ የዘወትር እጣፋንታችን ሆኗል፡፡

ከሁሉ ይባስ ብሎ ግን ተስድስት ወር በፊት ግምበኛ የሆንኩበት (ሙያተኛ ሆኘልሀለሁ)ወደ ሰማይ ጭምቡል ያለ ህንጣ ላይ የሚያሰራን አለቃ እኛ ስናረፍድ ከደመወዛችን ላይ ለመቆነጣጠር የማያመነታውን ያህል ደመወዝ እንደልቡ ሲያዘገይብን ትንሽ እኳ አይከነክነውም፡፡ ኧረ ማዘግየት ብቻም አይደል ተያ የባሰ ግፍ ይሰራብናል፡፡ የዛሬ ወር የሆነውን ላጫውትህ፡፡

ስራ አፈር ድሜ በልተን ጨርሰን ካስረከብን በኋላ ክፍያ ስንጠብቅ ሌላ ተጨማሪ ስራ ይኮናተርና ‹‹አዲሱን ስራ ጀምሩ ፤ የክፍያ ሂሳብ ሰረቸ ለዋናው አለቃ ልኬዋለሁ ዛሬ ወይ ነገ ይደርሳል›› ይለናል፡፡ እንግዲህ ምግብ በዱቤ እየበላንና እዳችን እየተቆለለ በዚያ ላይ የቤት ክራይ ምንከፍለው አጥተንና ቀኑ አልፎ ከአከራይ ጋር አዩኝ አላዩኝ ጠዋት ማታ በድብብቆሽ እየተሳቀቅን ግን አዲሱን ስራ እየሰራን በተስፋ ስንጠብቅ እሱም ዛሬ ነገ እያለ ሳምንታት ያጉላላናል፡፡

መጨረሻ ሲብስብን ስራ አቁመን ‹‹ደመወዛችንን ውለድ›› ብለን ስናፋጥጠው ‹‹ዋናው ተቋራጭ ገንዘብ አለቅልኝ ብሎ እኮ ነው፡፡ የናንተ ጉዳይ እኮ ሌት ተቀን ያስጨንቀኛል፡፡ ድርጅቱ ገንዘብ ባለመልቀቁ እኔም እንደእናንተው በችግር ነው ያለሁት፡፡›› ብሎ አንጀታችንን ሊበላ ይቃጣዋል፡፡

‹‹ስራ በውል መሰረት ተሰርቶ ካለቀ ድርጅቱ ምን አርጉ ብሎ ነው ገንዘብ የማይለቅ?›› ብለን ስንወጥረው ‹‹ዛሬን ብቻ ታገሱ፡፡ ስራ ግን መቆም የለበትም፡፡ ይኸን ስንጨርስ ለሁላችሁም ሸጋ ክፍያ ያለው አዲስ ስራ ተዋውያለሁ፡፡›› ይለናል፡፡

ይኸኛው ወጣት አሰሪያችን ደግሞ የእኛ መራብና መጠማት፣ ከተከራየነው ቤት ወደ ጎዳና መወርወራችን ሳይታየው <<ስራ ግን መቆም የለበትም>> ይለናል፡፡ ምን በልተን፣ በየትኛው ጉልበታችን ልንሰራለት?መቸም አንተ የአያ ዳርጌ ወፍጮ እንኳያለ ውሀ ሲንዶቀዶቅ አይተህ እንደማታውቅ እርግጠኛ ነኝ፡፡ አስትንፋስ ያለውን ሰው በባዶ ሆድህ ስራ ማለት እንግዲህ ምን የሚሉት ስልጣኔ እንደሆነ እንጃ፡፡

ታዲያልህ በነጋታው ስራ አቁመን የድርጅቱ ትልቁ ኃላፊ ዘንድ ኸደን ‹‹ደመወዝ ይከፈለን›› ብለን አቤቱታ አሰማን፡፡ ሰውየው አለባበሳቸው ሸጋ፤ ቁመናቸው ሎጋና ደልደል ያሉ ጎልማሳ፣ እንደ ጨ()ስ አደመ ሸጋ ግርማ ሞገስ ያላቸው ናቸው፡፡ በቀለም ትምህርት ብዙ የዘለቁና ዘመናዊ አኗኗር ያበሰላቸው እንደሆኑ ገና አይኔ እንዳረፈባቸው ነበር የገመትኩት፡፡ ግምት ብቻ ሆኖ ሊቀር፡፡

እሳቸው ወዳጀ….ገና የነተበና ላም አመንዥካ የተፋችው የሚመስል የስራ ልብሳችንን እንደለበስን ከፊታቸው ቆመን ሲያዩ ‹‹እናንተ ደሞ ምንድር ናችሁ? እዚህ ምን ትሰራላችሁ?›› ብለው ፊታቸውን ቋጥረው አንድባንድ ባይኖቻቸው ገላመጡን፡፡ ረሀብና ብሶት ናላውን ያዞረው ሰራተኛ ሁሉም አቤቱታውን ያለወረፋ ያንደቀድቅባቸው ጀመር፡፡ የሳቸው ጆሮ ሁለት የሚንጫጫው ምላስ መቶ ሆኖ ነገርየው ቅጡን ማጣት ሲጀምር ሰውየው በቁጣ ሁሉንም ጸጥ አደረጉት፡፡ አየህ… የተቋጠረ ገንዘብና የተቋጠረ ቂም ባዶውን ከተከማቸ ሰውና ህግ ሳይፈረጥሙ አይቀሩም፡፡

ለጥቀው በቁጣ እንደጋሉ ‹‹ይህ የስራ ቦታ እንጅ የማንም ወሮ በላ መፈንጫ አይደለም፡፡ ለመሆኑ ከድርጅቱ ጋር ቀጥተኛ የስራ ውል ያለው አለ?›› ብለው ጠየቁን፡፡ እኛም የኛን አሰሪ ጠቅሰን ለድርጅቱ የሰራነውን አስረዳናቸው፡፡

ታዲያ እሳቸውም ‹‹በእርግጥ ድርጅቱ ከልጁ ጋር ተዋውሏል፡፡ ስለዚህ ግንኙነታችሁ ከእሱ ጋር እንጂ ይህ ድርጅት እናንተን አያቃችሁም፡፡ ለተሰራው ስራ ደግሞ በውላችን መሰረት ተገቢውን ክፍያ ፈጽመናል፡፡ እናንተም ጉዳያችሁን ከሱ ጋር ጨርሱ፡፡ አለበለዚያ እዚህ የስራ ቦታውን እንረብሻለን ብትሉ ፖሊስ ጠርቸ እያንዳንድሽ ትታጎሪያታለሽ፡፡››

ልጁ በእለቱ ስራ ቦታ አልመጣም፡፡ ስልክ ስናቃጭልለትም አይመልስም፡፡ ይህን ለሰውየው ተናግረን ሚበላ ሚጠጣ እንዳልቀመስን፣ ከኪራይ ቤታችን ተወርውረን ጎዳና ልናድር እንደሆነ ብናስረዳና መላ እንዲፈልጉልን ብንማጠናቸውም ‹ወይ ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ› ሆኑብን፡፡

መጨረሻ ላይ አዝነን ስንባዝን አንድ ሰው የሰራተኛ ጉዳይ ሚባል መስሪያ ቤት አለ ብሎ ቦታውን ጠቁሞን ወደዚያው አቀናን፡፡ እዚያም በደላችንን ስናስረዳ አንድ ጠልጠል ያለ ወጣት የህግ ምሁር ወረቀትና እስክረቢቶውን መዥልጦ የስልጣን ማስታወቂያ ካርዱን በሰለሎ አንገቱ አጥልቆና ደረቱ ላይ አንጠልጥሎ ‹‹ኑ ተከተሉኝ›› አለን፡፡ እኛም ልባችን በተስፋ እየደለቀች ወደ ግምባታ ቦታው አጅበነው ተጓዝን፡፡ እጥር ግቢው ስንደርስ ጥበቃዎች እኛን እንዳያስገቡ ጥብቅ ትዛዝ እንደተሰጠነግረው አሰቆሙን፡፡ ወጣቱ የሰራተኛ ጉዳይ ባለሙያ ‹‹ሁለት ተወካይ ምረጡና እኔና ተወካዮቻችሁ ገብተን ጉዳዩን እንጨርሳለን፡፡›› አለ፡፡ እገሌ ተወካይ ይሁን አይ እሱ ንግግር አይችልም እገሌ ይሁን በሚል ስንጨቃጨቅ አንዱ ያንዱን ምርጫ እያጣጣለ የጋራ መከራችንን ተረስቶ በማይረባ ነገር ልንባላ ደረስን፡፡

የህግ ባለሙያው በሁኔታችን እየተቃጠለ ‹‹ብትስማሙ ተስማሙ! አለበለዚያ ጥያችሁ እሄዳለሁ፡፡ መስሪያ ቤቴ እንደናንተ አገልግሎቴን የሚጠብቁ ብዙ አሉ፡፡›› ሲል ገሰጠን፡፡ እኛም ምርጫ ስናጣ ሁለት ሰዎች እንደነገሩ መርጠን ላክን፡፡ አንዱ ተወካይ እኔ ነበርኩ፡፡

የድርጅቱ ኃላፊ ቢሮ ስንደርስ ጠሀፊያቸው ወጣቱን የህግ ሰው ሰላምታ ሰጥታ እኛን ገላምጣ ‹‹ሰውየው ስብሰባ ገብተዋል›› አለች፡፡ ባለሙያው እንደሚቆዩ ወይም እንደማይቆዩ ጠይቋት እሷም እንደማታውቅ ነገረችውና ተቀምጠን ለመጠበቅ ተወሰነ፡፡ ከአንድ ሰዓት በላይ ተጎለትን፡፡ ችጋር ያጎሳቆላቸው ሰርተው የላባቸውን የተነፈጉ ቢጤዎቼም በር ላይ ተኮልኩለው ይጠብቃሉ፡፡ ስንቱ ድሀ እንዲህ እየተጉላላ ቅማል የማይገድል ስብሰባቸው ላይ ተጥደው በሰው ብሶት የሚሳለቁ ስንት አሉ መሰለህ ወዳጄ አያ ሻረው፡፡

ሁለት ሰዓት የሚሆን ጠብቀን ሰውየው ሊያናግሩን መጡ፡፡ አሁንም በዚያ ጨካኝ አይናቸው እያዩን ‹‹የህግ ሰው ይዛችሁ መጣችሁ? እናንተ ሰዎች ገደባችሁን አታውቁም፡፡ ከዚህ ድርጅት ጋር ምንም ግንኙነት የላችሁም ስላችሁ አትሰሙም? ከህግ ባለሙያው ጋር መነጋገር እንችላለን፡፡ እናንተ ግን ከቢሮየ ውጡ፡፡›› አሉን፡፡

የህግ ሰውየው ሊያግባባቸው ሞከረ፡፡ <ወይ ፍንክች> አሉ፡፡ ባለሙያውም ምርጫ ሲጠፋ ‹‹ግድ የለም በቃ እኔ አናግራቸዋለሁ፡፡ እናንተ ውጭ ጠብቁኝ አለን፡፡›› እየከፋን ወጣንላቸው፡፡ ትንሽ ቆይተው ባለሙያውና ሰውየው እየተሳሳቁ ወጡ፡፡ ‹‹አየህ ድርጅታችን የአሰሪና ሰራተኛ ህጉን ብቻ ነው ተከትሎ የሚሰራው፡፡›› እያሉ ይደሰኩሩለታል፡፡

ወደኛ ተጠግተው አሁንም በንቀትና ጭካኔ እየገላመጡን ‹‹ጉዳያችሁን ተነጋግረን አንድ ውሳኔ ላይ ደርሰናል፡፡ አሰሪያችሁን ተደዋውለን ጠርተን ደመወዛችሁን እናስከፍላለን፡፡ እሱ ካልተገኘ ግን እኔ የድርጅቱ ስም በእንዲህ አይነት ነገር እንዳይነሳ ስለምፈልግና ይህን የህግ ሰው ላለማድከም ስል በድርጅቱ ኪሳራ እንዲከፈላችሁ አደርጋለሁ፡፡ እዚህ የምትመጡት የዛሬ ሳምንት ነው፡፡ ከዚያ በፊት ድርሽ እንዳትሉ፡፡ አይሆንም ካላችሁ ግን የፈለጋችሁት ፍርድ ቤት ድረስ መክሰስ ትችላላችሁ፡፡›› አሉን፡፡

የህግ ባለሙያውም ‹‹እኔ ልረዳችሁ የምችለው እዚህ ድረስ ነው፡፡ ሳምንት መጠበቅ ካልቻላችሁ የጠፋውን አሰሪያችሁን በፍርድ ቤት መጠየቅ ነው ያላችሁ አማራጭ›› ብሎን ውልቅ አለ፡፡

እናም ይኸውልህ ወዳጀ አያ ሻረው ዛሬን ምንበላው፣ምንጠጣው፣ ምናድርበት አጥተን የላባችንን ጠብታ ይዞ ዱካውን ያጠፋ ግፈኛ አሰሪያችንን እየረገምን በድርጅቱ ኃላፊ ቸርነት የሚሰጠንን ክፍያ ሳምንት እስኪደርስ እንጠብቃለን፡፡

እኔ ግን <ስራ ስራ ነው፡፡ ያለስራ ወትም አይደረስም> የሚል ፈሊጥ አለኝ፡፡ ይህን ታላሰብኩ በስተርጅና እዚህ ምን ልሰራ መጣሁ? ገንዘብ ቢጠፋ ህልም ግን አይጠፋም፡፡ ህልም ታለ ደግሞ ወኔ አይጠፋም፡፡ ወኔ ታለ ስራ አለ፡፡ ስራ ታለ ልቅምቃሚም ቢሆን ገንዘብ አይጠፋም፡፡ ያ…ጉፍንት አሰሪያችን አጭበርብሮ ጠፋ ብየ እድሜ ልኬን አንገት ደፍቸ ሳለቅስ አልኖር፡፡ ፍርድ ቤት ከሶ ለመከራከርም አቅም ያስፈልጋል፡፡ ሰውየውን ለመክሰስ አንቀጥ ጠቅሶ የሚጥፍ ሰው እንኳ ወጪው ደመወዙን ለተነፈገ ሰው ቅዠት ነው፡፡

ታዲያ ሁሉንም ትቼ ሰልስትና ትራንስቦርት ሰልፉ ላይ ተገትሬ አዲሱ ስራየ በግዜ ገባሁ አልገባሁ እያልኩ መጨነቁና መንቆራጠጡ ሳያንሰኝ ወረንጦ እጁን ወደ ደረት ኪሴ አሹሎ እየቆሰቆሰ እንደ ልጅነት ወዳጅ ከኋላየ የሚተሻሸኝን ሰውየ አፈር ድሜ ላስበላው ዞር ስል የአያ ጓሉ መቁረጫ ልጅ ደንገለው ሆኖ አላገኘው መሰለህ፡፡ ያብማይቱን ‹‹የማናባቱ ልኩን የማያውቅ ብቅብቅ ውርጋጥ ነው?›› ብየ በያዝኩት አካፋ ላቆነዳው ዞር ስል ደንገለው፡፡

ዛድያ ደም ፍላቴ ሁላ ጥሎኝ ብን አለ፡፡ ‹‹ኧሮግ እታታ፡፡ አንተ ነህ እንዴ ደንገለው? እኔ ደግሞ የማን ወሮ በላ ነው ብየ፡፡ አንተ… ኸምኔው እንዲህ ጠበደልህ?›› ብለው ትንሽ አንኳ ሳይደነግጥ ‹‹ሰውየ ምንድር ነው ምታወራው?›› ብሎኝ እርፍ፡፡ እንዲያው እጢየ ነው ዱብ ያለው፡፡ ኸሱ በኋላ የተሰለፉት ሰዎች ‹‹ማይኮ ትተዋወቃላችሁ? ምንሽ ነው?›› ብለው ቢጠይቁት ‹‹አላውቀውም›› ብሎ ሸመጠጠ፡፡ ደንገለው እንደሆነ ጥርጣሬ ባይገባኝም በከተማ ስም ስለጠሩት ትንሽ ተደናገረኝ፡፡

ከደንገለው ወደ ማይኮ ግን ትንሽ መንገዱ አላጠረም? እያልኩ እራሴን ስሞግት ወዲያው ከፊት ከኋላየ የተሰለፈው ህዝብ ‹‹ሞላጫ… ሌባ….የሚያ ውቅህ መስሎ ሊያታልልህ… ሊሰርቅህ ነው፡፡ አውቀው የገጠር ሰው እየመሰሉና ገና ከክፍለ ሀገር መጣን እያሉ የሚያጭበረብሩ በዝተዋል፡፡ ተጠንቀቁ›› እየተባባሉ ያም ያም ሲገለማምጠኝ ቆሌየ እንደተገፈፈ ሰልፉን ጥየ በእግሬ ማዝገም ጀመርኩልህ፡፡

እውነት እልሀለሁ ይህ ከተማ የማያሳየው ጉድ የለም፡፡ ደንገለው ካች አምና ሳውቀው ምላስ ነበር የሚያክል፡፡ አሁን እንደሰንጋ ሻኛ አውጥቶ፣ እናት አባቱ ያወጡለትን ስም በሰልባጅ ቀይሮና ኮረኮሯ ላይዋ ላይ እንደኮቸረባት የጎፈየች በግ ጠጉሩን አጎፍሮ የሰው ኪስ ሲጎረጉር ይውልልሀል፡፡ እንዲያው በራሴ ላይ ባይደርስ አላምንም ነበር፡፡ ደሞ እሱ ብቻ እንዳይመስልህ ስሙን የቀየረው፡፡ ቀያቸውን በለጋነታቸው ለቀው የመጡ ሴት ጉብላሊቶቻችን እነ ታንጉት ሁሉ አጓጉል የመሸታ ስራ ላይ ባክነው መቅረታቸው ሳያንስ ስማቸውም ‹ዚጢጢ ፣ቢጢጢ፣…› እየተባባሉ ምናለፋህ የ‹ጢ› ቅራቅንቦ ሆነውልሀል፡፡

እና ቀለም የዘለቀውና ቀለም የነካካው ተመሀይሙ ጋር ተደባልቀው ስልጣኔያቸውም ድንቁርናቸውም አልገባኝ ብሎ እንዲሁ እንደዠበረርኩ ቀረሁልህ፡፡ ወይኔ ሰውየው? ተመልሸ እንዳልመጣ እጀ ሞፈር መጨበጥ ረስቷል፡፡ እዚሁ እንዳልቀር ከነፋሱ እኩል መንፈስ አልቻልኩም፡፡ እንዲያው ምክር ቢጤ ካለህ እጠብቃለሁ፡፡

ወዳጅህ

 

 

Published in መዝናኛ

 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ አገራት የሚያገለግሉ ቆንስል ጀኔራሎችና በዋና መስሪያ ቤት የሚሰሩ ዳይሬክተር ጄኔራሎችን ሾሟል።

በዚህም መሰረት በቆንስል ጄኔራልነት የተሾሙት

1. አምባሳደር ዋህደ በላይ-በባለ ሙሉ ስልጣን ሚኒስትር ማዕረግ በሊባኖስ የቤይሩት የኢፌዴሪ ቆንስል ጄኔራል

2. አቶ ደመቀ አጥናፉ -በባለ ሙሉ ስልጣን ሚኒስትር ማዕረግ በህንድ ሙምባይ የኢፌዴሪ ቆንስል ጄኔራል ሆነው እንዲሰሩ ተሹመዋል።

3. አቶ ተፈሪ መለሰ- በባለ ሙሉ ስልጣን ሚኒስትር ማዕረግ በቻይና ጓንጁ የኢፌዴሪ ቆንስል ጄኔራል

4. /ሮ እየሩሳሌም አምደማሪያም - በባለ ሙሉ ስልጣን ሚኒስትር ማዕረግ በተባበሩት አረብ ኤምሬት የዱባይ የኢፌዴሪ ቆንስል ጄኔራል

በዋና መስሪያ ቤት በዳይሬክተር ጄኔራልነት የተሾሙት ደግሞ

 

1. አምባሳደር ሙሃሙድ ድሪር- የጎረቤት አገራትና ኢጋድ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል

2. አምባሳደር ነጋ ጸጋዬ- የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል

3. አምባሳደር አባዲ ዘሞ - የጎረቤት አገራትና የኢጋድ ጉዳዮች የሚኒስትሩ አማካሪ

4. /ር አምባሳደር መሃመድ ሃሰን- የፖሊሲ ምርምርና ትንተና ዲፓርትመንት ዋና አማካሪ

5. አምባሳደር ብርቱካን አያኖ- የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል

6. አቶ መላኩ ለገሰ- የእቅድና በጀት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል

7. አቶ አዛናው ታደሰ- የአለም አቀፍ ድርጅቶች ዳይሬክተር ጄኔራል

8. አቶ ብርሃኔ ፍስሃ -የሰንዓ ፎረም እና የኤርትራውያን ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ዳይሬክተር ጄኔራል

9. አቶ ኤፍሬም ብዙአየሁ- የአለም አቀፍ ህግ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል

10. አቶ ሽብሩ ማሞ- የፋይናንስና የግዥ ማኔጅመንት ዳይሬክተር ጄኔራል

11. አቶ ዘላለም ብርሃን -የቢዝነስ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄኔራል

12. አቶ አየለ ሊሬ- የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል

13. አቶ በሪሁን ደጉ- የኢንፔክተር ጄኔራል ጽ/ቤት ዳይሬክተር ጄኔራል

 

 

 

 

 

Published in ፖለቲካ

   

ፌዴራሊዝም የሚለው ቃል ‹‹Foedus›› ከሚለው የላቲን ቃል የተወረሰ መሆኑን መጻህፍት ይነግሩናል፡፡ ትርጉሙም ቃል-ኪዳን፣ ኮንትራት፣ ድርድር ወይም የአብሮነትና በጋራ የመኖር ውልን ይወክላል፡፡

ቃሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውልም በሰው ልጅና በፈጣሪ መካከል ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት ለመግለፅ ነበር፡፡ በጥንታዊ ዘመን በተለያዩ ትናንሽ ግዛቶች የሚኖሩ ማህበረሰቦች ራሳቸውን ከወረራና ከተለያዩ አደጋዎች ለመጠበቅ ሲሉ ውስጣዊ ማንነታቸውንና አከባቢያዊ ግዛቶቻቸውን እንደጠበቁ የጋራ አስተዳደርና ሕብረት ለመፍጠር ይስማሙ ነበር፡፡

ይህንን በፈቃደኝነት የመሰረቱትን ሕብረት የሚገልፅ ቃል በሚፈልጉበት ጊዜም ፌደራል ወይም ፌደራሊዝም የሚል ቃል ተስማሚ ሆኖ አገኙት፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ቃሉ የፖለቲካ ትርጉምና ይዘት እየወረሰ በመምጣት በ1291 የተመሰረተው የስዊስ ኮን-ፌደራላዊ ስርዓትና ከዛ ቀጥሎ የተመሰረቱ ፌደራላዊ ስርዓቶች ሕብረታቸውንና የመንግስታቶቻቸውን ቅርፅ ለመግለፅ ቃሉን እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡

ስለሆነም ፌደራላዊ የመንግስት አወቃቀር ማለት የራስ-አስተዳደርና የጋራ-አስተዳደርን ያጣመረ፣ ሁለት ወይንም ከሁለት በላይ የሆኑ መንግሥታት የሚፈጥሩት በቃል ኪዳን የሚመሰረትና የሚመራ አጋርነት ነው፡፡ አጋርነቱ በመካከላቸው ሊኖር የሚገባውን የሥልጣን ክፍፍልና ዝምድና ይወስናል፤ አንዱ የሌላውን ቅንነትና የአብሮነት መኖር እሳቤ ተቀብሎ በማመን ላይ ይመሰረታል፡፡ እንዲሁም አንዱ የሌላውን ልዩ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ወዘተረፈ በማክበርና በእኩልነት ይጠብቃል፡፡

ፌዴሬሽኖች ባለፉት ሁለት ምዕተ ዓመታት በተፈጠሩ የተለያዩ ታሪካዊ ክስተቶች ተፈጥረዋል፡፡ ከዓለም ህዝብ መካከል 40 በመቶ የሚሆነው የሚኖርባቸው 28 የዓለማችን ሀገራት የፌዴራሊዝም ስርዓትን ይከተላሉ፤ወይንም ፌዴራላዊ ተብለው ተፈርጀዋል፡፡ እነዚህ ሀገራት እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሰፊ ግዛት ያላቸው መሆናቸውና ዴሞከራሲያዊ ስርዓትን መከተላቸው ፌዴራሊዝም ከነጻነትና ከዴሞከራሲያዊ መረጋጋት ጋር ሊጣመር ችሏል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ስር ተመዝግበው ካሉ 192 ሀገራት መካከል 28ቱ ፌዴራላዊ ስርዓትን የሚከለተሉ ናቸው፡፡ ብዙዎቸ እንደሚያስቡት ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ ብቻ ያለ አንድነትን ሳይሆን ልዩነትን የሚያሰፋ ስርዓት አይደለም፡፡ ስርዓቱ ይህንን የማድረግ እድሉ እጅግ አናሳ ነው፡፡ ፌዴራሊዝም ሀገርን የሚበታትንና አንድነትን የሚያጠፋ ቢሆን ኖሮ ከኢትዮጵያ በፊት ፌዴራሊዝምን ቀድመው የጀመሩት ሀገራት ህልውና እስከዛሬ አክትሞ በነበር፡፡

እውነታው ግን ለቅል ነው፡፡ ፌዴራሊዝም ብዙነትን በአንድ ላይ አጣምሮ የሚይዝ ስርዓት ነው፡፡ እነ አሜሪካና ስዊዘርላንድ ፌዴራላዊ ሰርዓትን ተቀብለው መተግበር ከጀመሩ ምዕተ አመት አስቆጥረዋል፡፡ እንደ ተባለው ስርዓቱ ሀገርን አደጋ ውስጥ የሚጥልና አንድነትን የሚያጠፋ ቢሆን ኖሮ ዛሬ አሜሪካም ሆነ ስዊዘርላንድ የሚባሉ ሀገራትን ላናይ አንችል ነበር፡፡ ኢትዮጵያም ከዚሁ ተምራ ስርዓቱን አዲዎስ ማለት ትችል ነበር፡፡ እንደተባለው እውነታውና ስጋቱ ውሃና ዘይት ናቸው፡፡

አሜሪካ እአአ በ1789 በህገ መንግስት የተረጋገጠ ፌዴራላዊ ስርዓትን በሀገሯ ላይ እውን አድርጋለች፡፡ ስዊዘርላንድ ደግሞ እአአ በ1848 ስርዓቱን በህገመንግስቷ እውቅና አሰጥታ ዘርግታለች፡፡ ጀርመንም እአአ በ1871 ፌዴራላዊ ህገ መንግስትን ይፋ አድርጋለች፡፡

በመቀጠልም ካናዳ፣ ቤልጂየም፣ ህንድ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ሱዳን፣ አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ሜክሲኮ፣ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የተለያዩ ግዛቶች፣ ቼኮስሎቫኪያ፣ ከኮሚኒዝም መፈራረስ በኋላ ደግሞ ሶቪየት ህብረት ወደ ፌዴራል ሰርዓት በሂደት ተቀላቅለዋል፡፡

ፌዴራል ስርዓቶች የራሳቸው መሰረታዊ ባህርያት አሏቸው፡፡ እንደ አብነትም ከህዝባቸው ጋር ቀጥታዊ ግንኙነት ያላቸው ሁለት መንግስታት፣ ሕገ-መንግስታዊ ዋስትና ያለው የስልጣን ክፍፍል፣ የተፃፈ ሕገ-መንግስት፣ ክልሎች ወይንም ብሄር ብሄረ-ሰቦች የሚወከሉበት ሁለተኛ ምክር ቤት፣ ገላጋይ ተቋም የሚሉት ባህሪያቸው መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

የፌዴራል አወቃቀር የተጀመረው ከሶስት ሺ 2ዐዐ ዓመታት በፊት በእስራኤሎች እንደሆነ ታሪክ እማኝ ነው፡፡ ፌዴራል ሥርዓት እንደ ጥሩ የመንግሥት አወቃቀር አማራጭ እየታየ በመምጣቱም በርካታ ሀገራት በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያና ከ2ዐኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ መከተል ጀምረዋል። 21ኛው ክፍለ ዘመን የፌዴራል ሥርዓት ክፍለ ዘመን እንደሚሆን ይታመናል፡፡ የዚህ ምክንያቱ በርካታ ቢሆንም ብዙ ፀሃፊዎች የሚጠቅሱት የሚከተሉትን ነው፡፡

በዓለም ላይ በአሁኑ ወቅት የፀጥታ ችግርና የመስፋፋት አደጋ እየተበራከተ ነው። ይሄንን ለመመከት ጠንካራ የመከላከያ ሐይል ማስፈለጉ የግድ ነው። ለዚህ ደግሞ ፌዴራሊዝም ተመራጭ ስርዓት ነው። በዚህ ምክንያት ፌዴራሊዝምን ከተገበሩ አገራት መካከል ካናዳ፣ ጀርመን፣ ህንድ፣ ማሌዢያ በአብነት ይጠቀሳሉ። ሰፊ የጋራ ገበያና ኢኮኖሚ የመፍጠር ፍላጎትን ለመመለስም ፌዴራሊዝም ተመራጭ ስርዓት ነው። ካናዳ እና የአውሮፓ ህብረት ደግሞ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ። አንድነትን ከብዙነት ጋር አጣምሮ ለማስቀጠል፣ ርዕዮተ-ዓለማዊና ለድህረ-ቅኝ ግዛት መፍትሄ መሆኑም ፌዴራሊዝምን የማይተው ያደርገዋል። ኡጋንዳና ናይጀሪያ ጥሩ እማኝ ናቸው። ለድህረ-ግጭት መፍትሄ መሆኑም ሌላው የፌዴራሊዝም ስርዓት ተመራጭ ባህሪው ነው። አሜሪካ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካን በአብነት መጥቀስ ይቻላል። ትልቅ የቆዳ ስፋት ላላቸው አገራትም የሚስማማ አወቃቀር እንደሆነ የዘርፉ አዋቂዎች ከጻፏቸው ሰነዶች መረዳት ይቻላል።

የፌዴራል አወቃቀር በሶስት አይነት መንገድ ሊከሰት ይችላል። በፊት ነጻ የነበሩ መንግስታት በስምምነት አንድ የጋራ መንግስትና አገር ሊመሰርቱ ይችላሉ፡፡ በአንድ ማዕከላዊ መንግስት ይተዳደሩ የነበሩ ሀገራት በሚገጥማቸው ውስጣዊ ችግር ስልጣንን ከፍለው ወደታች በማውረድ ፌዴራል አወቃቀርን ሊከተሉና አንድነትን ሊያስቀጥሉ ይችላሉ፡፡ ሁለቱን በማዳበልም የፌዴራል ስርዓትን መመስረት ይቻላል፡፡

የፌዴራል ስርዓት አወቃቀር ዓይነቶች የሚባሉት ሶሰት ናቸው፡፡ እነዚህም ብሔራዊ /ጂኦግራፊያዊ አወቃቀር/ ሕብረ-ብሔራዊ /ብሔራዊ ማንነት፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ወዘተን… መሰረት ያደረገ/ እንዲሁም ሁለቱን ያዳበለ አወቃቀር የሚሉት ናቸው፡፡ ከእነዚህ የፌዴራሊዝም አይነቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እየተተገበረ ያለው ሕብረ- ብሄራዊ ፌዴራል ስርዓት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይሀ የፌዴራሊዘም አይነት ለቡድን ማንነት እውቅና የሚሰጥ ነው፡፡ የቡድን ማንነት መገለጫዎች የሚባሉት ደግሞ ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ታሪካዊ አመጣጥ፣ ማህበራዊ መስተጋብር ወዘተ የሚሉት መሆናቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሕብረ-ብሄራዊ ፌዴራል ስርዓት መነሻዎች የማንነት (የብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ … ወዘተ/ ጭቆና፣ የመልማት መብት መነፈግ፣ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዓፈና፣ የመልካም አስተዳደር እጦት ናቸው፡፡ እነዚህ ጭቆናዎች ለመጣል የኢትዮጵያ ህዝቦች በብሄር ጥያቄ ዙሪያ ተደራጅተው የፊውዳሉን ስርዓትና የደርግ ወታደራዊ አገዛዝን ለመጣል ታግለዋል፡፡ በ1983 .ም የኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተር ለማፅደቅ የተሰባሰቡ፣ እንዲሁም የሽግግር መንግስትን የመሰረቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ከሞላ ጎደል በብሄር ማንነት የተደራጁ ነበሩ፡፡ ትግሉም ከተቋጨ በኋላ እነዚህ ኃይሎች የሽግግር መድረክ በማቋቋም የጋራ ቻርተር አጽድቀዋል፡፡

የሽግግር መድረኩ ተልዕኮውን ካጠናቀቀ በኋላ በ1987 .ም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሊመሰረት ችሏል፡፡ በመሆኑም የፌዴራል ስርዓቱ የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ሙሉ በሙሉ በመመለስ አዲስ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነቶችን መፍጠር ችሏል፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት ያልተመለሱ ጥያቄዎች የሉም። ህገ መንግስቱ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥያቄዎችን መልሷል፡፡ አንድነት ያስቀጠለ ስርዓትን ወልዷል፡፡ መድብለ ፖርቲን ዕውን አድርጓል፤ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትንና የማህበራዊና መሰረተ-ልማት አውታሮች ልማትን ያረጋገጠ ስርዓት ፈጥሯል፡፡

በኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ላይ አንዳንድ ጥያቄዎች ወይንም ቅሬታዎች ሲቀርቡበት ይሰማል፡፡ እነዚህ ቅሬታ የሚያቀርቡ አካላት በአንድ በኩል ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራል ስርዓቱ አንድነትን አደጋ ላይ ይጥላል ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ህብረ-ብሄራዊ ስርዓቱ የብሄሮችና ብሄረሰቦች መብቶችን አላረጋገጠም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

በስርዓቱ ላይ ከሚቀርቡ ትችቶች መካከልም የተወሰኑትን መጥቀስ ይቻላል። ‹‹ዓንቀጽ 39 ለህብረታችን ተፈላጊ ድንጋጌ አይደለም፣ ፌዴራል ስርዓቱ ውጤታማ የሚሆነው ጂኦግራፊያዊ አወቃቀርን መሰረት ካደረገ ነው፤ ፌደራላዊ አወቃቀር በባህሪው ለአንድነት አደጋ ነው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ትኩረት ከአንድነት ይልቅ የቡድን መብትን በመጠበቅ ላይ ያተኮረው፤ ፌዴራል ስርዓቱ አገር አቀፍ የነበረውን ግጭት ወደ ትናንሽ ግጭቶች ቀይሯቸዋል፤ ስርዓቱ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት እኩል አላረጋገጠም፤ በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶች የዚሁ ውጤቶች ናቸውና” ወዘተ የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡ ነገር ግን የስርዓቱን መሰረታዊ መርሆዎችና ያስገኟቸውን ውጤቶች በመተንተን የተጠቀሱት ጉዳዮች ትክክል እንዳልሆኑ ማየት ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ከሌሎች ፌዴሬሽኖች የሚለይባቸው ጉዳዮች አሉት፡፡ ከብዙው በጥቂቱ እነዚህን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ተረጋግጧል፤ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሆነዋል፤ እነዚህ ህዝቦችም በፌደሬሽን ምክር ቤት እንዲወከሉ እድል ተፈጥሯል፤ ሕገ-መንግስትን የመተርጎም ስልጣንም ለፌደሬሽን ምክር ቤት ተሰጥቷል፡፡ ይህ ባህሪው የኢትዮጵያን የፌዴራል ስርዓት ከሌሎች ለይቶታል አስብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርዓት የወደፊት አቅጣጫዎችም አሉት፡፡ እነዚህም የመከባበር፣ የመደማመጥ፣ የመቻቻል፣ የመደጋገፍና የመተባበር ባህልን ማጎልበት፣ ብዙሀነትን ማክበር፣ የጋራ ማንነት መገለጫዎችን ማጎልበት፣ የመንግስታትና የህዝቦች ግንኙነቶችን ማጠናከር፣ ሕገ-መንግስትና ሌሎች የስርዓቱ ሕጎችን ማክበርና መጠበቅ፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ መላ ሃብትን ማንቀሳቀስና መረባረብ፣ ጎጂ የውጭ ፖለቲካን (Imported Politics) ማስወገድ፡፡

ወደ መበታተን አደጋ ውስጥ የነበረች አገር በፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር ምክንያት ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪኳ አለምን ያስደመመ የኢኮኖሚ እድገት ልታስመዘግብ ችላለች፡፡ ‹‹…ማደግ እንደምንችል ያረጋገጥነው፤ የማደግ ተስፋችንም በእጃችን እንዳለ ያመንነው በፌዴራል ስርዓታችን ነው›› ሲል መንግስት የሚከራከረውም በአየር ላይ እንዳልሆነ መሬት ላይ ያሉ እወነታዎች ይናገራሉ።

እንደ አጠቃለይ የፌዴራሊዝም ስርዓት በተለያዩ የአለማችን ሀገራት ተመራጭነቱ እየጨመረ ነው፡፡ ለዚህም የራሱ ምክንያቶች አሉት፡፡ በዋናነት ለብዝሃነት ዕውቅና የመስጠት ዝንባሌ እያደገ መምጣቱ፣ህብረ ብሄራዊነትና ህብር ሉአላዊነት መስፋፋቱ፣ ዘረኝነት ኋላ ቀር አስተሳሰብ እየሆነ መምጣቱ፣ የተለያየ ቋንቋ ባህልና እምነት ያላቸው ነገር ግን ተፈቃቅረውና ተከባብረው የሚኖሩባት ሀገር ለመፍጠር እና ራሳቸውን ለማስተዳደር ማስቻሉ እንዲሁም አንድነትን ለመገንባት ጎሳን ማጥፋት የሚለው የአሃዳዊ ስርዓት መክሰሙ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

ፌዴራሊዝም ለብዝሃነት እውቅና የሚሰጥና አንድነትን ይበልጥ የሚያጠናክር ሰርዓት ነው፡፡ ከዚሀ ውጪ የሚደመጡት ፌዴራሊዝም ሀገርን ይበታትናል ወይንም አንድነትን ያጠፋል የሚሉት አስተያየቶች ‹‹ያላዋቂ ሳሚ....››ያሰኛሉ፡፡ ምክንያቱም ስርዓቱ በኢትዮጵ የተመረተ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ የተተወ አይደለምና ነው፡፡

 

በጋዜጣው ሪፖርተር

 

 

Published in ፖለቲካ

 

በጎንደር ከተማ ዙሪያ ከሚገኘው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ቆላድባ የወትሮው ጭር ያለ እይታው ደብዝዟል። አካባቢው በርካታ ቁጥር ባላቸው የተሽከርካሪ አይነቶች ተጨናንቋል። የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች፣ ከፌደራል እና ከክልሉ የመጡ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በስፍራው ማልደው ተገኝተዋል። እነዚህ አካላት ከስፍራው ለመገኘታቸው ደግሞ አንድ የጋራ ምክንያት ነበራቸው። ይሄውም ለዘመናት በንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ሲሰቃይ ለነበረው ነዋሪ መፍትሄ ያነገበው የጎንደር ንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የመጠናቀቁ ብስራት የሚሰማበት እለት መሆኑ ነበር።

የልማቱ ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን ተከትሎ የድል አድራጊነት ስሜት ያዘለ የደበዘዘ፣ ያልተሟላ ደስታ የሚነበብበት የፊት ገፅታ ይነበብባቸዋል። ይሄውም የነዋሪዎቹ ደስታ ምልዑ እንዳልሆነ ያሳብቃል። ምክንያቱ ምን ይሆን? የሚል ጥያቄንም ያጭራል፤ ጠየቅንም። የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችም ለማስረዳት ወደ ኃላ አላሉም።

በሰሜን ጎንደር ዞን አዘዞ ከተማ ግራር ሰፈር በሚባለው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ መዝገበ አረጋዊ የውሃው ጥያቄ መልስ በማግኘቱ የተሰማቸውን ደስታ ይገልጹና። አሁንም መልስ የሚሹ ሌሎች የልማት ጥያቄዎች መኖራቸውን ይገልጻሉ። አዘዞ ከተማ እና አካባቢዋ ላይ የኃይል መቆራረጥ እያደረሰ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በማንሳት ችግሩን በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኙ ከተሞችም ተመሳሳይ መሆኑን ይናገራሉ። "በከተማዋ ያሉ በርካታ ወፍጮ ቤቶች፣ ሆቴሎች፣ የውበት ሳሎኖች እና ሌሎች የንግድ ቤቶች ግብር ለመክፈል እጅ እስኪያጥራቸው ድረስ የችግሩ ሰለባ ሆነዋል። ብርት ጥፍት የምትለው መብራት በቀን ውስጥ ከአስር ጊዜ በላይ ትጠፋለች። የመብራት መቆራረጡ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን የማቃጠሉ ሁኔታ የመብራቱ ሌላው መዘዝ ነው። ይህም በአካባቢው ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ ከማኮላሸት በዘለለ፤ መንግስት በሚሰበስበው ግብር ላይ ጥቁር ጥላ የጣለም ጭምር ነው” ብለዋል አቶ መዝገበ።

«የውሃ ህይወትነት ያለብርሃን ያልተቋጨ ሩጫ ነው» ሲሉ የመብራት አገልግሎት እንደሌለ በመግለፅ ንግግራቸውን የሚጀምሩት በሰሜን ጎንደር ዞን ደረስጌ ማርያም ቀበሌ ገበሬ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጥላሁን መለሰ ናቸው። አቶ ጥላሁን እንደሚሉትም፤ የአካባቢ ጥያቄ ሁለት ነው። የንፁህ መጠጥ እና የመብራት ጥያቄ። ለበርካታ ዓመታት ከቀበሌ ደረጃ እስከ ክልል በመሄድ ጥያቄውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ቢዘገይም የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥያቄው ምላሽ አግኝቷል። የቀረው የመብራት ጥያቄ ስለሆነ በተቻለ ፍጥነት መልስ ሊያገኝ ይገባዋል።

ልጆቻችን በቅርብ ርቀት የቀለም ትምህርት እንዲያገኙ በአቅራቢያችን ትምህርት ቤት ተገንብቶልናል። ነገር ግን ዛሬም ድረስ ልጆቻችን ጥናታቸውን የሚያጠኑት በኩራዝ ነው። ሴቶች ምግብ ለማብሰል አሁንም እንጨትን ይጠቀማሉ። ይሄ ሁኔታ በእርግጥም አሁን ካለንበት ዘመን እና ከአገራችን ሁኔታ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም" ሲሉ ይናገራሉ፤ አቶ ጥላሁን።

አስተያየት ሰጪው አያይዘውም፤ «በርካታ የገጠር አካባቢዎችን መንግስት የመብራት ተጠቃሚ ማድረጉን እየሰማን ነው። ከጎንደር ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ላይ ተቀምጠን መብራት አልተመለከትንም። መንግስት ሁኔታውን ተገንዝቦ እና አጥንቶ የመብራት ተጠቃሚ አድርጎን ከችግሩ እንድንወጣ እንጠይቃለን» ሲሉም በተማፅኖ መንግስት ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ።

የጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት መላኩ ተካ ደግሞ የመብራት ችግር በአካባቢው ለመፍጠር የሚቻለውን የስራ እድል እያኮላሸው መሆኑን በሌላ ወገን ያነሳል። እንደ እርሱ ማብራሪያ፤ በአካባቢው በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች ይገኛሉ። የወረዳው መስተዳድር ወጣቶቹን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ማለትም በጣውላ ስራ፣ በዳቦ ቤት፣ በፀጉር ስራ እና ሌሎች የስራ ዘርፎች እንዲሰማሩ ታሳቢ በማድረግ መንቀሳቀስ ተችሎ ነበር። ይሁንና በአካባቢው ያለው የመብራት አገልግሎት ችግሩ ጥረቱ ከመንገድ እንዳስቀረው በቁጭት ይናገራል።

በጎንደር ከተማ ቀበሌ 17 ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ጣይቱ ወርቅነህ ደግሞ ጎንደር ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ታሪክ ያላት ከተማ ናት፤ የንግድ ማዕከልና የቱሪዝም መዳረሻ ከተማ ብትሆንም ከተማዋ እንደ ጥንታዊነቷና ታሪካዊነቷ ትኩረት ተሰጥቷት አልለማችም ይላሉ።

«ከተማዋ በቱሪዝሙ ዘርፍ ብቻ ከፍተኛ እድገትና ተጠቃሚ የምትሆንበትን መሰረት መዘርጋት ይቻላል። ይሁንና መገኘትና መሆን በሚገባው ልክ ቱሪዝሙን የሚያነቃቁ የመሰረተ ልማት ስራዎች እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች የሉም። እነዚህና መሰል ዕገዛ ቢደረግላት ኖሮ ታድጋለች፤ ነዋሪዎቿም ተጠቃሚ ይሆኑ ነበር። አሁንም ጊዜው አልረፈደም ብዙ መስራት ይጠይቃል እንጂ» ሲሉ ወይዘሮ ጣይቱ ሀሳባቸው ቋጭተዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ነዋሪዎች ይህንን ሲሉ መንግስት በአካባቢው እያደረገ ያለውን የልማት ተግባር አይክዱም። ለአብነት ያህልም የከተማውን የመናኸሪያ ቦታ ጥበት ለማቃለል ታስቦ በ69 ሚሊዮን ወጪ የተገነባው የአዘዞ ዘመናዊ የአውቶብስ መናኸሪያ ግንባታ ተጠናቆ መመረቁ ለከተማው ነዋሪዎች ደስታን የፈጠረ ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ 870 ሚሊዮን ብር በጀት የተመደበለት የአዘዞ አርበኞች አደባባይና የ12 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ በእለቱ በይፋ መጀመሩም ሌላው የልማት ቱሩፋት ሆኗል።

መንግስት በጤናው፣ በመንገድ፣ በትምህርት ቤት ግንባታ ላይ ሰፊ ስራዎችን በማከናወን ማህበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሄደበት ርቀት መኖሩን አንስተው አመስግነዋል። በኢኮኖሚው ዘርፍም ቢሆን በኢንቨስትመንት፣ በጥቃቅን እና አነስተኛ እና ሌሎች የልማት ተግባራቶችን በማከናወን ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ከመልካሙ ስራ ጋር አብረው የሚጠቅሱት ነው። በእነዚህ የማህበራዊ ፍላጎቶች እጥረት ምክንያት የሚደርሱና ሊደርሱ የሚችሉ መቃወሶችን በእነኝህ ልማቶች መቀረፉ የጎንደር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች አልዘነጉም። በተጠቀሱት የልማት ዘውጎች መንግስት እንዳከናወነው የልማት ተግባራት ሁሉ በቀሪዎቹ የልማት ጥያቄዎች ላይ አፋጣኝ ምላሹን እንዲሰጥ አጥብቀው ይሻሉ።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባው አቶ ተቀባ ተባበል፤ በነዋሪዎቹ የቀረቡትን የልማት ጥያቄዎችን እና ቅሬታዎች ተገቢነት ይቀበላሉ። አያይዘውም እንዳሉት፤ ለዘመናት ጥያቄ የነበረውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥያቄን ለመመለስ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ዘግይቶም ቢሆን በቆላ ድባ የተገነበው የጎንደር ውሃ ፕሮጀክት ምላሽ ሰጥቷል። የነበረውን የንፁህ መጠጥ ውሐ ችግር በመቻልና በትግስት በመጠበቅም የተግባሩን ውጤት ለማጣጣም መቻሉን ተናግረዋል። የህብረተሰቡን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ በትጋት እንደሚሰራ በመጠቆም፤ በአሁኑም ወቅት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ የሚያስችለው ጥረት ተጀምሯል ይላሉ።

መብራት ያልተዳረሰባቸው አካባቢዎችንም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ተጨማሪ የማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ እየተካሄደ በመሆኑ ችግሩ በዘላቂነት ይፈታል ብለዋል። ከንቲባው በከተማዋ ያሉ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች እንደዘገዩ አምነው፤ ከአሁን ወዲህ ከህዝቡ ጋር በመተባበር ጥያቄዎችን ለመመለስ ሁለንተናዊ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

«በጎንደር ከተማ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ በሚደረገው ርብርብ እና ጥረት ላይም ህብረተሰቡ ጥያቄውን በትግስት እንዳቀረበው ሁሉ፤ መንግስት ችግሩን ለመፍታት ከሚያደርገው ጥረት ጋር በአብሮነት መስራት አለበት» ሲሉም አቶ ተቀባ ለከተማው ነዋሪዎች መንግስት የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ተሳትፏቸው የማይተካ ሚና እንዳለው በጥያቄም መልክ አቅርበዋል።

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የጎንደር ህዝብ አንዱና ትልቁ ጥያቄው ምላሽ አግኝቷል። ምላሽ የሚሹ ሌሎች በርካታ ጥያቄዎቹን በተገቢው ጊዜና በተቻለው ፍጥነት ምላሽ ለመስጠት ክልሉም ሆነ ከተማ አስተዳደሩ በጥምረት ይሰራሉ ብለዋል።

 

ዳንኤል ዘነበ

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ከግራ ወደ ቀኝ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢንጃሚን ኔታነያሁ፤

 

እስራኤል እንደ አገር ከቆመች ዛሬ ልክ 69ኛ ዓመት ሆናት በራቀው ዘመን አይሁዳውያን በዓለም ዙሪያ በተለያዩ አገሮች ተበትነው ይኖሩ ነበር፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ 40 ሺህ አይሁዶች በዛን ጊዜዋ ፍልስጤም እንዲሠፍሩ ተደረገ፡፡ በተለያዩ ጊዜዎችም የሠፋሪዎቹ ቁጥር እያደገ መጣ፡፡ በተለይም በ2ኛው የዓለም ጦርነት ሂደት በአይሁዶች ላይ ቁምስቅልና መከራቸው መብዛቱ የራሳቸውን አገር የማበጀት አስፈላጊነቱን አጐላው፡፡ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ የአይሁዳውያኑ ቁጥር ከአጠቃላይ የፍልስጤም ምድር ነዋሪዎች 33 በመቶ ደረሰ፡፡ ከጦርነቱ ሁለት ዓመታት በኋላ የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ በአይሁዶችና በፍልስጤማውያን አረቦች መካከል ከጊዜ ወደጊዜ እያየለ የመጣውን ግጭት ለማስወገድ የዛኔዋ ፍልስጤም በአይሁዶችና በአረቦች ይዞታነት ለሁለት እንድትከፈል ወሰነ፡፡ ከወራት በኋላ ነፃ የእስራኤል መንግስት ታወጀ፡፡ ይሄ ከሆነ 69ኛ ዓመታት ተቆጠሩ።

የእስራኤል ነፃ መንግስትነት ያስቆጣቸው እንደ ግብፅ፣ ሶሪያ፣ትራንስዮርዳኖስና ኢራቅ በማግስቱ ከእስራኤል ጋር ወደ መዋጋቱ ገቡ፡፡ በዚህ ጦርነት አረቦቹ ተሸነፉ፡፡ ከዚያ ሁለት አስር ዓመታት በኋላ በአረቦችና በእስራኤል መካከል ሌላኛው ጦርነት ተቀሰቀሰ፡፡ የእስራኤልና የአረቦች ጦርነት የሚባሉት ጦርነቶችን ከተካሄዱ 44 ዓመታት ሆኗቸዋል፡፡ ከእስራኤልና አረቦች ተደጋጋሚ ጦርነቶች በኋላ ፍልስጤማውያን ከነፃ መንግስትነት እንደራቁና ለዚህም እንደጣሩና እንዳለሙ ይኖራሉ፡፡መሬት ለሰላም የተሰኘው የሰላም ስምምነት ፍቱን መፍትሄ ነው ተብሎ ተስፋ ተጣለበት፡፡ የስምምነቱ ፈራሚ የቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ይስሃቅ ራቢን የዚያን ጊዜው የውጭ ጉዳይ ሚንስትራቸው ሺሞን ፔሬዝና የፍልስጤማውያኑ የነፃነት መሪ ያሲር አራፋት በኦስሎው ስምምነት መልካም አደረጋችሁ ተብለው የኖቤል የሰላም ሸልማትን ተቀበሉ፡፡ ስምምነቱ ስራ ላይ ሳይውል ይስሃቅ ራቢን ተገደሉ።

የፍልስጤማውያኑ መሪ ያሲር አራፋትም የናፈቋትን ነፃይቱን ፍልስጤም ሳያዩና ሳይደርሱባት አለፉ፡፡ በእስራኤልና በፍልስጤማውያን መካከል አልፎ አልፎ ጦርነት አካል ግጭቶች ሲቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ ብዙውን ጊዜ ግን አካባቢው ጦርነትም ሰላምም የሌለበት ሁኔታ ፍጥጫና ምንጊዜም ስጋት እንዳንዣበበበት ቀጥሏል። የሁለቱን አገራት የእርስ በእርስ ግንኙነት ወደ ሰላም ለማሻገር የአለም አገራት በየጊዜው ጥረት ቢያደርጉም ተሳካ ሲባል እየከሸፈ አመታት አልፈዋል።

ባሳለፍነው ዓመት ፈረንሳይ በእስራኤልና ፍልስጤም መካከል ተቋርጦ የነበረውን የሰላም ውይይት ተመልሶ እንዲያንሰራራ ስታደርግ የነበረውን ጥረት ማስታወስ ይቻላል። የአሜሪካ፣ የሩስያ እና የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ወደ ፓሪስ በመጥራት የሁለቱን ወገኖች ጉዳይ ወደ አለም አቀፍ አጀንዳነት ለመመለስ ስትሞክር የቆየችው አጋጣሚ ለዚሁ ማሳያ እንደሆነ አልጀዚራ ያመላክታል። ከተቋረጠ ሶስት አመት የሆነው የእስራኤልና ፍልስጤም የሰላም ድርድር በሁለት ሀገራት ውይይት ደረጃ እንዲቀጥል አዲሱ የትራምፕ አስተዳደርም እያደረገ ያለው ጥረት ማሳያ ሊሆን ይችላል። ይሁንና የአለም አገራት በእስራኤልና ፍልስጤም ጉዳይ ላይ ለውጥ ማምጣት አልተቻላቸውም።

ከሰሞኑ የአለም ታላላቅ የመገናኛ ብዙሃን ደግሞ የሁለቱን አገራት ወዳጅነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚቀይር ከስተት መፈጠሩን በስፋት በዘገባቸው ዳሰውታል። የአሜሪካው መሪ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ ለዓመታት ተግባራዊ ሳይደረግ ሲንፏቀቅ የኖረውንና አሜሪካ ቴላቪቭ ከተማ ላይ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ወደ እየሩስአሌም የማሸጋገር ጉዳይ ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተደመጠው ይህ ጉዳይ አገራቱ ሰላም እንዲያሰፍኑ እየተደረገ በሚገኘው ጥረት ላይ ጥቁር ጥላውን የሚጥል ይሆናል ሲል የዘገበው ሲኤን ኤን ነው። አሜሪካ የሁለቱ አገራት ጉዳይ ከምንም በላይ ያገባኛል በሚል ስሜት ሰላምን ለማውረድ ላለፉት 20 ዓመታት በጽኑ አቋም ስትታትር ቆይታለች።አገራቱን ወደ ተሻለ ሁኔታ ለማድረስም ያስችላሉ ያለቻቸውን የመፍትሄ ሃሳቦችን በጊዜው በነበሩት መሪዎቿ በማቅረብ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን ዘገባው አስታውሷል።

በትራምፕ የፕሬዝዳንትነት ዘመንም ይሄው ሁኔታ የቀጠለ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ አሜሪካ ላለፉት 20 ዓመታት በጽኑ አቋም ስታሳየው ከነበረው የሁለት ሀገርነት የመፍትሔ ሃሳብ የተለየ ሆኖ ታይቷል። በወቅቱ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በእስራኤል እና ፍልስጤም ጉዳይ ላይ በሁለቱም ወገን ተቀባይነት ካለው፤ የአንድ ሀገርነት መፍትሔም ይስማማኛል ሲሉ የአገራቱን ሰላም ለመመለስ ትራምፕ በሚያደርጉት ጥረት ላይ በጎ ፍንጭ ያሳየ ክስተት ተብሎለት ማለፉንም ዘገባው ጠቅሷል።

ዘ ኢንዲፔንደንት በሌላ ወገን ጉዳዩ የእስራኤል እና የፍልስጤምን ትኩሳት ዳግም የቀሰቀሰና አሜሪካ አገራቱን ለማስማማት በምታደርገው ጥረት ላይ ጥላሸት የሚጥል እንደሆነ በስፋት ዳሶታል። ዘገባው እንዳሰፈረው፤ ለአስተዳደሩ ምናልባትም ኤምባሲውን የማዘዋወር ሂደቱን መጀመሩ የሚኖረው አደጋ አነስተኛ ቢመስልም፤ ነገር ግን አሜሪካ አገራቱን ለማስማማት በምታደርገው የሰላም ድርድር ላይ ትልቅ ተጽእኖ የሚኖረው ነው።

የሲኤንኤን ዘጋቢው አሮን ዴቪድ ሚለር እየሩሳሌምን እንደ እስራኤል ዋና ከተማነት እውቅና መስጠቱ አደጋው ከፍተኛ መሆኑን በትንታኔው አቅርቧል። ከዚሁ ጋር በማያያዝም የአሜሪካን በእስራኤል እና ፍልስጤም ድርድር ፍትሃዊ መስመር የመያዙ ሃቅ ላይ ጥያቄ የሚፈጥር እንደሆነ በዘገባው ተዳስሷል። በዶናልድ ትራምፕ ዘመንም ከአድሎአዊነት በነፃ መልኩ ለአገራቱ የጋራ ጥቅም ዘብ ቆሜያለሁ የምትለውን አሜሪካንን ልብ መርምሮ ያሳየ ክስተት ሆኗል ተብሏል። አገራቱን ለማስማማት የምታደርገው ጥረት የእስራኤልን ጥቅም ለማስከበር ያለመ መልክ አለው ወደሚል መደምደሚያ የሚያደርስ እንደሆነም ሲኤን ኤን ፅፏል።

የእስራኤል እና ፍልስጤም የዘመናት የደም መፋሰስ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ እየሩሳሌም የእኔ ምድር ነች የሚለው የሁለቱ አገራት ክስ ነው። አሜሪካ ኤምባሲዋን ወደ እየሩሳሌም የማዘዋወሯ ጉዳይ ለእስራኤል እውቅና እንደመስጠት የሚቆጠር መሆኑንም ዘገባው አስፍሯል።

ዶናልድ ትራምፕ ወደ ነጩ ቤተመንግስት ለመምጣት ባደረጉት የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ኤምባሲውን የማዘዋወሩ ጉዳይ አንዱ አጀንዳቸው ነበር። ይሄንንም በቅርቡ አደርገዋለሁ በማለት ቃል መግባታቸውን ዘገባው አስፍሯል። ባሳለፍነው እሮብ እለት አሜሪካ ኤምባሲዋን ከቴላቪቭ ወደ እየሩሳሌም ታሸጋግራለች በማለት ይፋዊ መግለጫ በመስጠት ቃላቸውን መጠበቃቸውን ለማሳየት እየጣሩ እንደሆነ ዘገባው አመላክቷል። ይህ ውሳኔ ግን በፍልስጤም እና በእስራኤል ድንበር ደም መፋሰስ የሚያስከትል መሆኑን ዘግቧል።

ቢቢሲ በሌላ በኩል ዶናልድ ትራምፕ እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ መሆኗን በቀጥታ እውቅና አይስጡ እንጂ በተዘዋዋሪ እንደማረጋገጫ የሚቆጠር ነው ሲል ዘግቧል። ይህንን ንግግራቸውን ተከትሎም ከአረቡ አለም አገራት በኩል ተቃውሞ መሰንዘሩን በመረጃው አካቷል። የከተማይቱ ዕጣ ፋንታ በእስራኤል እና በአረቦች መካከል ከሚፈጠሩ እኩይ ችግሮች አንዱ ነው። በመሆኑም የአሜሪካ የእየሩስአሌምን ዋና ከተማነት ለእስራኤል ማረጋገጫ የመስጠቱ ዳፋ በቀጠናው ለተኩስ እና ለደም መፋሰስ ምክንያት እንደሚሆን ምንም እንደማያጠያይቅ ቢቢሲ ዘግቧል።

1995 አሜሪካ በእስራኤል ቴላቪቭ ከተማ ላይ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ወደ እየሩስአሌም ለማዘዋወር ከእስራኤል ጋር መፈራረሟን በማስታወስ የዘገበው ደግሞ ሲ ኤን ኤን ነው። አሜሪካ ፍላጎቷን በወቅቱ ይፋ ታድርግ እንጂ ተግባራዊ ለማድረግ ሳትችል በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። የአሁኑ ፕሬዝዳንት ትራምፕን ጨምሮ ባለፍት 22 ዓመታት አሜሪካንን የመሩት ፕሬዝዳንቶች ሁሉም በእስራኤል ቴላቪቭ ከተማ የሚገኘውን ኤምባሲውን ለማዘዋወር የስምምነታቸውን ፊርማ አኑረዋል። ይሄው ጉዳይም የአሜሪካ ኮንግረንስ በሚያደርገው ስብሰባ ሁሉ አጀንዳ ሆኖ በመቅረብ ውትወታው ሳይቋረጥ ዘልቋል። ይሁን እንጂ ስምምነቱን ወደ ተግባር ለመቀየር ያሰበ እንጂ የተገበረ መሪ ግን አልነበረም ሲል ፅፏል።

ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰነዘሩትን አስተያየቶች እና ተቃውሞች ለማስተባበልም አሜሪካ እየሞከረች መሆኗን የዘገበው ደግሞ ሮይተርስ ነው። ፕሬዝዳንት ትራምፕ በጉዳዩ ላይ አቋማቸውን አይናገሩ እንጂ፤ በአገሪቱ ፀጥታ ጉዳይ የዋይት ሃውስ አማካሪው ማችማስተር ውሳኔው በአገራቱ ህልውና ላይ ተፅእኖ የሚኖረው እንደማይሆን መናገሩን ሮይተርስ በዘገባው አስፍሯል።

 

ዳንኤል ዘነበ

 

 

Published in ዓለም አቀፍ

 

በመጪው ዓርብ ህዳር 29 ቀን 2010/12ኛው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሰመራ ከተማ ይከበራል። በዚህ በዓል ምናልባት ከሦስት ሺህ የማያንሱ የሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ልዑካን ይገኛሉ። በዚህ የልዑካን ቡድን ውስጥ የባህል ልዑካን ዋነኞቹ ናቸው። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚከበሩ ህዝባዊ በዓላት በሙሉ በዓላማው ትልቅነትና በድምቀት የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ቀን የሚያክል የለም።

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የተከበረው 8ኛ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ላይ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ የተከበረው 9ኛው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ላይ የመሳተፍ እድል አግኝቼ ነበር። በእነዚህ ሁለት በአላት ላይ ለቀናት በአንድ መንደር በሚሰፍሩት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መሃከል የሚታየው የመተዋወቅ ፍላጎት፣ መደናነቅና ወንድማማችነት ልዩ ስሜት የሚያሳድር ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በዓሉን ለማክበር ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለጥቂት ቀናት በሚሰፍሩበት መንደር በኢፌዴሪ ህገመንግስት መሰረት ሊገነቧት ቃል ኪዳን የተግባቡባትን በልዩነት ውስጥ ያለ ጠንካራ አንድነት ያላትን ኢትዮጵያ በስሜት ህዋሳችን መረዳት በሚያስችል ሁኔታ ሞዴሏን ማግኘት ይቻላል።

በተለይ በ2006 /ም በጅግጅጋ ከተማ የተከበረው 8ኛው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ልኡካን የሰፈሩበት በኢትዮጵያ ሱማሌ የባህል ቤቶች ያሉበት መንደር ኢትዮጵያን እንደ አንድ መንደር መመልከትና ማዳመጥ ያስቻለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የየብሄሮቹና ብሄረሰቦቹ ልዑካን ቡድኖች በመንደሩ ውስጥ በቆዩባቸው ሶስት ቀናት ምሽት በመንደሩ መሃከል ባሉ ክፍት ቦታዎች ላይ ሁሉም በየራሳቸው ባህላዊ ጭፈራ መንደሩን በተለያየ የዳንስና የዜማ ህብር ልዩ ውበትና ድምቀት ይሰጡት ነበር። ህብረ ብሄራዊቷ ኢትዮጵያ ታምራለች።

ዘንድሮ በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መዲና ሰመራ የሚከበረው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ከጅግጅጋው ጋር ተመሳሳይ ገጽታ የሚኖረው ይመስለኛል። ሰመራም ልክ እንደ ጅግጅጋው ሁሉ የአፋሮች ባህላዊ ጎጆዎች ችምችም ያሉበት መንደር አዘጋጅታ የኢትዮጵያ ብሄሮችን፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን በዚህ አንድ መንደር ውስጥ ለማስተናገድ እየተጠባበቀች ነው። ይህች መንደር ለሶስት አራት ቀናት ኢትዮጵያ ትሆናለች።

እንግዲህ፤ ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሃገር ብትሆንም ይህ ህብረ ብሄራዊነት በዘውዳዊውና በወታደራዊው ደርግ የመንግስት ሥርአቶች እውቅና ተነፍጎት መቆየቱ ይታወሳል። ዘውዳዊው ሥርአት የሁሉንም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ማንነት ጨፍልቆ አንድ ማንነት ያለው ኢትዮጵያዊነት የመፍጠር ስትራቴጂ ነበር የሚከተለው። ደርግም ይህንኑ ሥትራቴጂ በተጠናከረ ሁኔታ አስቀጥሎ ነበር። ይህ ስትራቴጂ ተግባራዊ በሆነባቸው አንድ ክፍለ ዘመን ያህል ጊዜ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ግብር በሚከፍሉበት ሃገር በቋንቋቸው የመንግስት አገልግሎት የማግኘት መብት ተነፍገዋል። ልጆቻቸው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መሰረት ትምህርት የማግኘት እድል ተነፍገዋል። ባህልና ወጋቸው እንደርካሽ ተቆጥሮ እንዲሸማቀቁ ተደርገዋል። በእነዚህ እርምጃዎች በገዛ ሃገራቸው ላይ በማንነታቸው አፍረው አንገታቸውን እንዲደፉ ያደረገ ሁኔታ ተፈጥሯል። ማንነታቸውን ለመደበቅ በተለይ ወደ ከተማ ሲገቡ በቋንቋቸው የወጣላቸውን የመጠሪያ ስማቸውን ለመቀየር ይገደዱ የነበረበት ሁኔታ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

ዘውዳዊው ሥርአት በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ላይ በወሰን ማስፋት ወረራ የተቆጣጠራቸው አካባቢ የነበሩ ብሄሮችን፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን የባለሃገርነት መብት ነፍጎ ነበር። ዘውዳዊው ሥርአት ሃገር የሚለው ህዝብን ሳይሆን መሬቱን በመሆኑ በተቆጣጠረባቸው አካባቢዎች የነበሩትን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የባለሃገርነት መብታቸውን ገፍፏል። ዘር ማንዘራቸው በኖረበት፣ አቅንቶ እያረሰ ሲተዳደር ዘመናትን ባስቆጠረበት መሬት ላይ የመሬት ባለቤትነት መብት ተነፍገዋል። ሰፍረው የሚኖሩበት መሬት ለመሳፍንቱ፣ መኳንንቱ፣ ለሥርአቱ ባለሟሎችና በየደረጃው ለነበሩ የመንግስት ተሿሚዎች ከነባለሃገሩ በርስትነትና ጉልት ተሰጠ። በገዛ መሬታቸው ላይ የባለርስትና ባለጉልት ገባር ጢሰኛ ለመሆን ተገደዱ። በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እስር ቤት ሆነች።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይህን መብትና ነጻነታቸውን የነፈገ እስር ቤት፣ ይሁን ብለው በጸጋ አልተቀበሉም። ታግለውታል። በመጀመሪያ ባልተደራጀና ግብታዊ በሆነ ሁኔታ በየአካባቢው ሹማምንት ላይ ያተኮረ ትግል ነበር የሚያካሂዱት። ይህ በየአካባቢው በልዩ አጋጣሚ ቀስቃሽነት በግብታዊነት ሲካሄድ የነበረ አመፅ አርሶ አደሩን ለጭፍጨፋና ለአደባባይ ግርፋት ከመዳረግ ያለፈ ውጤት ማስገኘት አልቻለም። ይሁን እንጂ የተደራጀና ስትራቴጂ ላይ የተመሰረተ የነጻነት የትጥቅ ትግል የተጸነሰው እዚህ ግብታዊ አመፅ ውስጥ ነበር። የቀዳማዊ ወያኔን፣ የባሌ አርሶ አደሮችን አመፅ ወዘተ ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል።

1960ዎቹ አጋማሽ በኋላ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብሄራዊ ነጻነታቸውን የማረጋገጥ ስትራቴጂ ላይ የተመሰረተ የተደራጀ የትጥቅ ትግል ማካሄድ ጀምረዋል። ዘውዳዊውን ሥርአት በተካው ወታደራዊ ደርግ የስልጣን ዘመን በብሄር ተደራጅተው የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ የነበሩ ቡድኖች ከሃያ በላይ ነበሩ። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በየአቅጣጫው የከፈቱት የነጻነት የትጥቅ ትግል በመጨረሻ አሃዳዊውን የደርግ ስርአት ዳግም ሊቆም በማይችልበት ሁኔታ ፈንቅሎ አስወገደው።

አዲሲቱ ኢትዮጵያ የነጻነት ትግል ሲያካሂዱ በነበሩት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተገነባች ሃገር ነች። የሃገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በሃይል ሳይሆን በፈቃዳቸው በመከባበርና በእኩልነት ላይ በተመሰረተ አንድነት አብረው ለመኖር ተስማምተው የመሰረቷት ሃገር ነች። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የየራሳቸውን ነጻ ሃገር ከመመስረት ይልቅ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተደዳሩ በእኩልነት የሚኖሩበትን ሃገር መመስረት መርጠዋል። ይህንን ምርጫቸውንም በህገመንግስት ቃል ኪዳን አስረዋል።

በህገመንግስቱ መግቢያ ላይ እንደሰፈረው ከዚያ ቀደም በክፉም በደግም የተጋሩትን የጋራ እሴቶች መነሻ በማድረግ፣ ተዛብቶ የነበረውን ታሪካዊ ግንኙነት በማስተካከል በመከባበርና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበር ለመመስረት ተስማምተዋል።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የአዲሲቱ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው። የኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 8 የህዝብ ሉዓላዊነት በሚል ርዕስ ስር፤«የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች፣ ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው።ይህ ህገመንግስት የሉዓላዊነታቸው መገለጫ ነው» ይላል።

እንግዲህ፤ በጽሁፉ መግቢያ ላይ ያነሳሁት በየዓመቱ የሚከበረው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያለፈ የቆሸሸና የተዛባ ታሪካቸውን አጽድተውና አስተካክለው፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት የሆኑበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመመስረት ቃል የተግባቡበት ህገመንግስት የጸደቀበትን ቀን መነሻ በማደረግ ነው የሚከበረው። ይህን ዕለት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድ መንደር የህብረ ብሄራዊቷን ኢትዮጵያ ሞዴል ፈጥረው የሚያከብሩት፣ አንድነትን የሚያጠናክር ዕለት ነው። ዕለቱ ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤትነት የተረጋገጠበት ዕለት በመሆኑ ትልቅ ዋጋ ይሰጠዋል።

 

ኢብሳ ነመራ

 

Published in አጀንዳ
Wednesday, 06 December 2017 17:50

እኛ ነን!

 

ኢትዮጵያ በታሪኳ ብዙ ውጣ ውረዶችን ወጥታለች፤ ወርዳለች። ወድቃለች፤ ተነስታለች። አዝናለች ተደስታለች። የእርስ በእርስ ጦርነት ያደረሰባት ድቀትም ቢሆን ዛሬም ድረስ በታሪኳ ገዝፎ ይታያል። ከነገስታቱ ዘመን ጀምሮ አንዱ ሌላውን ጥሎ ለማለፍ የተደረጉ ግጭቶች አገሪቷን ወደፊት ሳይሆን ወደኋላ ሲጎትታት ኖሯል። ይሄ እንደ አገር የምናዝንበት ታሪካችን ነው። ዛሬም ድረስ በቀደመው ታሪክ መግባባት ተስኖን በውስጥም በውጭም ሆነን ጎራ ላይተን የምንወቃቀሰው ማንም ሳይሆን እኛ ነን።

አንዱ የግዛት መስፋፋት የሚለውን ግጭት ሌላው ወረራ እያለ፤ አንዱ ማስገበር የሚለውን የግጭት መንስኤ ሌላው ዝርፊያ እያለ እየሰየመ እነሆ በዚህ ዘመን ላይ ሆነን እንኳን የዚያ ዘመን ታሪካችን ሳያግባባን እንዳለን አለን። ይሄ የማንም ታሪክ አይደለም የእኛ እንጂ። ከነገስታቱ ዘመን በፊትም ይሁን በኋላ በመጡ መንግስታት አንድ አገር፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ፣ አንድ በሚሉ ብዙ የአንድ ቅኝቶች አንድ የሆንን መስሎን አንድ ሳንሆን በተዛባ ግንኙነት የኖርነው አሁንም እኛ ነን።

ይሄ አገዛዝ ይብቃ ብለን ለ17 አመታት መራር ትግል አድርገን መራር መስዋዕትነት በከፈሉ የአገራችን የቁርጥ ቀን ልጆች ላብና ደም ህገ መንግስት የፃፍን ታሪክም ያጻፍን እኛ ነን። የግፍ አገዛዙን መሸከም ታክቶን መሳሪያ አንግበን በተለይም ለብዙሐነታችን እንቅፋት የነበረውን ስርዓት ታግለን ያስወገድን፤ የትግሉ ውጤትን እያጣጣምን ያለን፤ ተወስዶብን የነበረውን ነጻነት ያስመለስን፤ ተነጥቀን የነበረውን ማንነታችንንም ህገ መንግስታችን ላይ በሰማዕታት ደም ያጻፍን ማንም ሳይሆን እኛው ነን።

የሚላስ የሚቀመስ አጥተን በረሃብ አለንጋ የተገረፍን፤ ምፅዋዕት ፍለጋ አደባባይ የወጣን፤ ዓለም ስለ ረሀባችን የዘመረልንና የለመነልን እኛ እንጂ ማንም አይደለም። በተፈጥሮ ሀብት ብዛትና አይነት እንደ እኛ የታደለ፤ ሰፊ የሚታረስ መሬት፣ ከዓመት ዓመት የሚፈሱ እልፍ ወንዞች ያላቸው፣ ሰው ሰራሽም ሆኑ የተፈጥሮ ድንቅ መስህቦች ያሉባት አገር ባለቤት የሆንን፣ በሚሊዮን የሚቆጠር የትኩስ ጉልበት ባለቤት የሆኑ ወጣቶች ያሉን፣ በአግባቡ ብንጠቀምባት ትልቅ አንድነት የሚፈጥር ልዩነት ያለን ህዝብና አገር እኛ ነን።

በአሀዳዊ ስርዓት እየተመራች ማንነታቸውን ወደጎን እንዲሉ ይገደዱ የነበሩ ህዝቦች የነበሩባት አገር፣ በክልላቸው ውስጥ በራሳቸው ቋንቋ መስራትም ሆነ መማር፣ በክልላቸው ሀብት መጠቀምና ማዘዝ እርም የሆነባቸው ህዝቦች የነበሩባት አገር የነበረችን እኛ እንጂ ማን ሊሆን ይችላል። ማንም።

በከፈልነው መራር መስዋዕትነት ዛሬ ኢትዮጵያ ሲባል 76 በላይ የሆኑት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አዕምሯችን ውስጥ እንዲመጡ አድርገን አገራችንን እየገነባን ያለን እኛ ነን። በልዩነት ላይ የተመሰረተ አንድነት የሰፈነባት አገር እየገነባን እንደ ታሪኳ ሁሉ የገዘፈ የኢኮኖሚ እድገት እየተመዘገበባት ያለች አዲስ ኢትዮጵያ እየፈጠርን ያለነውም እኛ ነን። እኛ ብዙ ነን። እኛ ትናንትም ነበርን፤ ዛሬም እለን፤ ነገም እንኖራለን።

የትናንቱ ታሪካችንን እንደ ጥሩ መስፈንጠሪያ ቆጥረን ዛሬ በዓለም ዙሪያ የምንደመጥና የምንመረጥ አገር ሆነናል። በዓለም ላይ ነዳጅ ሳይኖራቸው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ አገራት ተርታ በቀዳሚነት የሚገኘው የአገራችን ስም ነው። ትናንት የለመንን እኛ፤ ዛሬ ባለ ሁለት አኃዝ ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት የሚዘገብባት አገር ባለቤት የሆነውም እኛ ነን።

የትናንቱ የልማት ቁጭታችን የዛሬውን ልማት ወልዷል። የዛሬው ልማታችን ደግሞ የነገዋን ኢትዮጵያን የማይፈጥርበት ምንም ምክንያት የለም። ምክንያቱም ከማንም ሳይሆን ከራሳችን የተማርነው ይሄንኑ ነውና። እርስ በርስ በተባላንበት ዘመን ተርበናል፤ እርስ በእርስ ተከባብረን በሰራንበት ዘመን ድርቅ እንኳን መትቶት ረሀብን ድል መትተናል። ይሄ የማንም ሳይሆን የራሳችን ታሪክ ነው። እኛ እንደዚህ ነን።

እየተመዘገበ ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ የጨረሰለት ያበቃላት እንዳልሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው። ስለሆነም አሁንም እኛ ይሄን ተግዳሮት አንድ ሁለት ብለን እንፈታዋለን፤ በተባበረ ክንድም እንረታዋለን። ከምንም በላይ ግን አገራችን እየገባችበት ያለው የሰላም ማጣት ጉዳይ ወደነበርንበት አረንቋ እንዳይመልሰን ያሰጋናል። ስጋቱ ግን ትጋት ካልታከለበት ዋጋ የለውም። ስለሆነም አብረን በወደቅንበት ዘመን አብረን ታግለን አሸንፈን ወደ ድል እንደመጣን ሁሉ፤ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች የእኛው ጉዳዮች ናቸውና አብረን የመፍትሄው አካል መሆን አለብን።

መንግስት ብቻውን የፈጠረው ችግር የለም፤ ብቻውን የሚፈታው ችግርም አይኖርም። ስለሆነም የፊታችን ህዳር 29 የቀን የሚከበረው የብሄሮች ብሄረሰቦች ቀን በዓልን ለዚህ አይነቱ ዓላማ ማዋል ይገባል። በዚህች አገር ላይ የነበርን እኛ፤ ያለነውም እኛ የምንኖረውም እኛ ነን ካልን፤ ለስኬቱም ለውድቀቱም አብረን እንወቃቀስ፤ አብረን እንስራ፤ አብረንም አገራችንን ወደፊት እናስኪድ። በልዩነታችን ሳይሆን በአንድነታችን ላይ እናተኩር፤ ከመንደር ፖለቲካ እንውጣ። ከግል ተጠቃሚነት ተላቅቀን ሁላችንም እኔ እኔን ትተን እኛ እኛ እንበል። ምክንያቱም እኔነት ይህችን አገር ወደ ግጭት እንጂ ወደ አንድነት ሲያመጣት አልተመለከትንም፤ ወደፊትም አንመለከትምም።

 

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።