Items filtered by date: Wednesday, 01 February 2017

 

የቪዥን ሶከር አካዳሚ ሰልጣኞች፤                                                    አቶ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ

 

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በርካታ ችግሮች ተደጋግመው መነሳታቸው እንግዳ ነገር አይደለም። ፌዴሬሽኑም ቢሆን ባለፉት ሃያ ዓመታት ከመገናኛ ብዙሃን የሰላ ትችት ያመለጠበትና የተሞገሰበት ወቅት አይታወስም። ብልጭ ድርግም እያለ በመጓዝ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ የስፖርት ቤተሰቡን ለማስደሰት ቀና ከማለቱ ዝቅ የሚያደርግ እንቅፋት አያጣውም።

የተተኪዎች ኮትኩቶ የማሳደግ ችግር ወትሮም እንከን የበዛበት ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ችግሩ ጎልቶ እየተነሳ ይገኛል። የስፖርት ቤተሰቡ፤ መገናኛ ብዙሃንና የስፖርቱ ባለሙያዎች ጩኸታ ቸውን በማሰማት መጪው ጊዜ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ጨለማ ዘመን እንዳይሆን ስጋታቸውን በመግለፅ ላይ ናቸው። ከሰላሳ አንድ ዓመታት ቆይታ በኋላ እኤአ 2013 ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈችው ኢትዮጵያ በዓለምና አህጉር አቀፍ ውድድሮች መርሃ ግብር ከማሟላት የዘለለ ጉዞ ማድረግ አለመቻሏ የሁሉም ስፖርት ቤተሰብ ቁጭት ነው።

በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ማለፍ በመቻሏና የተሻለ እንቅስቃሴ በማሳያቷ ታላቅ መነቃቃት ቢፈጠርም በመሰረተችው አፍሪካ ዋንጫ ዳግም ለመመለስ አሁንም ከአራት ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። ከመቶ ሚሊዮን ህዝብ በላይ እንደሚኖርባት የሚገመትባት ኢትዮጵያ አስራ አንድ ብቁ የእግር ኳስ ተጫዋች የመፈጠሩ ጉዳይ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሁኗል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በእግር ኳሱ የተወሳሰበ ችግር ውስጥ መኖሩን የሚጠቁሙ አሉ።

እግር ኳሳችን ላለማደጉ፤ የስልጠና ስርአታችን፤ ታዳጊ ተጫዋቾች ላይ ትኩረት ሰጥተን አለመስ ራታችን እንደሆነ ይጠቀሳል።እንዲሁም ክለቦች ታዳጊዎችን ከማፍራት ይልቅ አንጋፋ ተጫዋቾች ላይ ብቻ ማተኮራቸው፤ የክለቦች ኢንቨስትመንት ለትላልቅ ተጫዋቾች እንጂ ከታች ለሚመጡት ተጫዋቾች አለመሆኑ መሰረታዊ ነጥቦች እንደሆኑ በተደጋጋሚ ይነሳል። በተለይም ታዳጊ ተጫዋቾች ላይ ካለመስራት ብሎም ደረጃውን የጠበቀ የስልጠና ስርአት አለመዘርጋቱ ለእግር ኳሱ ችግር መንስኤ መሆናቸው በብዙዎች ዘንድ ይታመንባቸዋል። ይህንንም ተከትሎ ካለፉት አስምስት አመታት ወዲህ በርካታ የስፖርት አካዳሚዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ዘመናዊ የስልጠና ስርአት በመፍጠርና ታዳጊ ተጫዋቾችን በመኮትኮት የአገሪቱን የእግር ኳስ ችግር መፍትሄ ማበጀት አላማቸው አድርገው ከሚንቀሳቀሱት ተስፈኛ አካዳሚዎች ውስጥ የጨቅላ እድሜ ያለው ቪዝን ሶከር አካዳሚ አንዱ ነው።

ኢብሳ መሃመድ በዚህ አካዳሚ ልምምድ ከሚያደርጉ ታዳጊዎች አንዱ ነው።ወደዚህ አካዳሚ ያመጡት ወላጆቹ ሲሆኑ፤ከልጅነቱ ጀምሮ እግር ኳስን አብዝቶ እንደሚወድ በመረዳታቸው የስፖርቱን ፍቅር በተሟላ ስልጠና እንዲታገዝ ወደ ቪዝን አካዳሚ እንዳመጡት ይናገራል።ኢብሳ እንደሚለው ወደፊት እግር ኳስ ተጫዋች መሆን ይፈልጋል። ስለዚህ ታዳጊ አሰልጣኙ፤ተስፈኛ የክንፍ ተጫዋች እንደሆነ ነው ያረጋገጡልን።

የአራተኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ኢብሳ በእግር ኳሱ ብቻም ሳይሆን በትምህርቱም ከአንድ እስከ አምስትም ባለው ደረጃ እንደሚወጣም በመግለፅ ጠንካራ እንደሆነ ያብራራል። በትምህርቱም ይሁን በእግር ኳሱ ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ሁለቱንም አጣጥሞ እየተጓዘ እንደሚገኝም ነግሮናል።

እንደ ኢብሳ ሁሉ የወደፊት የእግር ኳስ ተጫዋች ህልምን ሰንቀው ወደ ቪዝን አካዳሚ ብቅ ካሉ በርካታ ታዳጊዎች መካከል ዳግም ዳንኤል አንዱ ነው።ታዳጊው እንደሚለው ስልጠናውን ከጀመረ አራት ወራት ተቆጥረዋል።ቀደም ሲል ከነበረኝ የመጫወት ብቃት ለውጥ አምጥቻለው።በስልጠና ወቅት የተለያዩ ልምምዶችን ነው የምናደርገው። አሰልጣኞችን እንደ ጓደኛ አቅርቦን ስለሚያሰራን ደግሞ የበለጠ ስፖርቱን በፍቅር እንድንሰራው አድርጎናል።እኔ ደግሞ ግብ ጠባቂ በመሆኔ ወደ ፊት እንደ አሰልጣኝ ደሳለኝ ትልቅ ግብ ጠባቂ ለመሆን ነው ፍላጎቴ።በዚህ ከቀጠልኩኝ ያሰብኩትን እንደማሳካ እተማመናለው፤ እሱም ያለኝ ይሄንን ነው» ሲል ነበር ተስፋውን ያጋራን።

14 አመቱ ዮሃንስ ተወልደ ብርሃን በዚህ አካዳሚ ከሚሰለጥኑ ታዳጊዎች አንዱ ነው።ለበርካታ ጊዜያት በሌላ አካዳሚ ልምምድ ያደርግ እንደነበር ያስታውሳል።ይህ አካዳሚ ሲከፈትም ልገባ ችያለው።እዚህ ከገባሁ አራት ያህል ወራትን አስቆጥሬያለው።ልምምዳችንን የምናደርገው ቅዳሜና እሁድ ነው። አሰልጣኞቻችን የተለያዩ ስልጠናዎች ይሰጡናል። ይህም የራሳችንን ብቃት ለማዳበር እየረዳን ነው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በአካዳሚው ጥሩ ብቃት ያላቸው ልጆች አሉ።ይህ ደግሞ የበለጠ የመጫወት አቅሜን እያሳደኩኝ እንድቀጥል አግዞኛል »ሲልም አስተያየቱን ቋጭቷል።

የቪዥን ሶከር አካዳሚ መስራች የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንና የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ፤ ቪዝን ሶከር አካዳሚ ከተመሰረተ ሰባት ወራት ያህል ተቆጥረዋል። ታዳጊዎችን በማሰባሰብ የአገራችንን እግር ኳስ ክፍተት ለመሙላት እየሰራን እንገኛለን።

«በአሁኑ ወቅት በአካዳሚውም 21 የሚሆኑ በተለያዩ የእድሜ ክልል የሚገኙ ታዳጊዎች ልምምድ እያደረጉ ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታ ወደፊት ውጤታማ እንሆናለን የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ።

አካዳሚውን የጀመርነው ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ነው።ለበርካታ ጊዜያት የመጀመሩ ሃሳብ ቢኖረኝም በተለያዩ ምክንያቶች ማሳካት ሳይቻለኝ ቆይቻለሁ። ለመጀመር እንቅፋት ከነበሩብን ነገሮች ደግሞ ዋነኛው የፋይናንስ አቅም ነው።እንደሚታወቀው ስፖርቱ ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ነው።ወደ ተግባር ለመግባት ደግሞ በእኔ አቅም ብቻ የሚሆን አይደለም። ይሁንና ጊዜው ደረሰና ተጫዋች ሆኜ ያደንቁኝ የነበሩ ግለሰቦች እንዲሁም ድርጅቶች ይህንን ሃሳብ ሲሰሙ ድጋፍ አደረጉልን።ከትጥቅ ጀምሮ ከኳስ ጀምሮ ድጋፍ አድርገውልን ወደ ተግባር ልንገባ ችለናል»ሲል ያለውን ፍላጎት ነግሮናል።

አገራችንን የገባችበትን የተተኪ ስፖርተኞች ችግር ለመቅረፍ የበኩሌን መወጣት ፍላጎቱ ነበረኝ የሚለው ደሳለኝ በዚህም በተጫዋችነት ጊዜዬ ያካበትኩትን ልምድ ማካፈል ፤ብሎም በሙያው አገሬን በመጥቀም አገራዊ ግዴታዬን መወጣት አንዱ መንገድ እንደሆነ አስብ ነበር።ለዚህም አንዱ መንገድ ብዬ ካሰብኳቸው ነገሮች ውስጥ አካዳሚን ከፍቶ የአገሪቷን የተተኪ ስፖርተኞች ችግርን ለመቅረፍ አስተዋፅኦ ማድረግ ነው።የተጫዋችነት ጊዜዬ እንዳበቃ አካባቢ ይህንን ሃሳቤን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ለማድረግ ጅማሮ አድርጌ ነበር። እንደሚታወቀው የስፖርት ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ በመሆኑ በእኔ አቅም የማይሞከር ሆኖብኝ ሃሳቡን እንደ ሃሳብ ይዤ ብቻ ለዓመታት ቆየሁ።ጊዜው ሲደርስም ሃሳቤን ወደ ተግባር ለመለወጥ እግሬን አነሳው።ጊዜ ለኩሉ አይደል የሚባለው ከአንድ ጓደኛዬ ጋር በመሆን አካዳሚውን ለመክፈት ቻልን።ይህ መሆን የቻለው ግን በእኛ አቅም ብቻ አልነበረም።ከጅማሮው ጀርባ የድጋፍ እጃቸውን የለገሱን ግለሰቦችና ድርጅቶች አሉ።

ቢቢቲ አይሞተርስ ባለቤት የሆኑት አቶ መሃመድ አወልና ጓደኞቹ አስተባብሮ ወደ 40 ሺ ብር አሰባስበው አርባ ያህል ኳሶችን ገዝተው አበርክ ተውልናል። ደስ ትሬዲንግ ካምፓኒ ደግሞ የተጫዋቾችንና የአሰልጣኞች ሙሉ ትጥቅ ገዝቶ አበርክቶልናል።እኔ ተጫዋች በነበርኩበት ወቅት በአድናቂዎቼ በኩልም ለሜዳ ማሰሪያና ለአንዳንድ ወጪዎች የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ አድርገውልናል። ከዚህ በተደማሪ ደግሞ ዩቴክ ኮንስትራክሽን ከፍተኛ እገዛ አድርጎልናል።አሁን ካደረገው እገዛ በተጨማሪም የአካዳሚው ቀጣይነትን ለማረጋገጥ ወደፊትም ስፖንሰር እንደሚሆነን ቃል ገብቶልናል።እንደ ዩቴክ ሁሉ አስገዶም ኮንስትራክሽን በቀጣይ ድጋፋቸው እንደማይለየን ቃል ገብተውልናል።በዚህ መልኩ የተጀመረው አካዳሚያችን በአሁኑ ወቅት በርካታ ታዳጊዎችን በተለያዩ የእድሜ ክፍል በመመደብ እየሰለጠነ ይገኛል።

እስካሁን ባለው ሂደት አካዳሚው ገና ጅማሮ ላይ ነው።ስለዚህ በውድድር ደረጃ ተሳታፊ መሆን አልቻልንም።በቀጣይ ጊዜያት ያሉት ልጆች ጠንካራ ልምምዶች ካደረጉ በኋላ በተለያዩ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ይሆናል።በተለይ በሚቀጥለው አመት ተሳታፊ የመሆን እቅድ ይዘን ነው እየሰራን ያለነው።

ከክለቦች ጋር ዘላቂ የሆነ ስምምነት አድርጎ አካዳሚዎች የሚያፈሯቸውን ታዳጊዎች ቢያቀርቡ ላቸው ጥሩ ነገር ይፈጠራል።ይህ ማለት በአሁኑ ወቅት አገራችን ላይ የምናየውን ዘመናዊ የስልጠና ስርአት ችግር ያቃልላል። በምትኩ በጥሩ የስፖርት ስልጠና ውስጥ ያለፈ ታዳጊ አገሪቷ ላይ እንዲበረክት እድል ይፈጥራል።በተጨማሪም አካዳሚዎች ጠንክረው ስልጠናቸውን መስጠት እንዲችሉ አቅም የሚፈጥር ነው። ስለዚህ እኛም እንደአካዳሚ ከክለቦች ጋር አብረን የምንሰራበትን ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት የምናደርግ ይሆናል።

በክለቦችም በኩል እየደከመ ያለውን የአገራችን ስፖርት ለመታደግ ጥረት ማድረግ ይገባቸዋል። ሃላፊነቱም አለባቸው። ከስር መሰረቱ የሚወጡ ታዳጊዎችን የማፍራት ስራ ላይ ማተኮር ይጠበ ቅባቸዋል።

አካዳሚውን ስንጀምረው አላማው የአገራችንን ስፖርት ማሳደግ ነው።ከአካዳሚዎች የሚመጡትንም ታዳጊዎች በመቀበልና አካዳሚዎችን መደገፍ ይኖርባቸዋል።ምክንያቱም ሃላፊነቱ የጋራ ነውና።

እንደ አጠቃላይ ፤ በእርግጥም በስፖርቱ ለውጥ ለማምጣት ሁሉም እዳ እንዳለበት እሙን ነው። የስፖርት ባለሙያው ያለውን ልምድ በሙያው ማካፈል፤ባለሃብቱም በገንዘቡ ስፖርቱን በተለያዩ መንገዶች መደገፍ፤ ክለቦችም ተስፋን ሰንቀው ላሉት ታዳጊዎች ቦታ በመስጠትና የተከደነ አይናቸውን በመክፈት፤ጋዜጠኞችም ታዳጊዎች ላይ የሚሰሩትን ስራዎችን ተከታትሎ ሽፋን በመስጠት፤በሌላም ሙያ ያሉ በስፖርቱ ተሳትፎ ሲያደርጉ ለውጡ አብሮ እንደሚመጣ እሙን ነው።

 

ዳንኤል ዘነበ

Published in ስፖርት

 

ዘመድ ጥየቃ ከሩቅ ስፍራ መጥተው ቤተሰቡን የተቀላቀሉት እንግዶች እጃቸው ባዶ አልነበረም። ለብዙሀኑ መስተንግዶ ይበጃል ያሉትንና ለክብሩ ጭምር የተጠነቀቁለትን ትልቅ ድፎ ዳቦ ይዘዋል። ከተቀመጠበት ሰፌድ በላይ በጉልህ የሚታየውና ለአይን የሚማርከው ይህ ድፎ እንዲቆረስ ሲቀርብ አይደለም ለእንደኔ አይነቱ ዳቦ አፍቃሪ ቀርቶ «ለድፎ ዳቦ እምብዛም ነኝ» ለሚል ሳይቀር መቼ በልቼው በሚል የሚያጓጓ ነው።

ቡና ተፈልቶና ጎረቤቶች ተጠርተው የተለመደው ምርቃትና ምስጋና እስኪጠናቀቅ ድረስ ትግስት አልነበረኝም ። በእርግጥ ይህ ይሆን ዘንድ አብሮን የቆየው ባህልና ልምድ እንደሚያስገድደኝ አልጠፋኝም ። የዛንዕለታ ዳቦውን ለመብላት የነበረኝ ፍላጎት ግን የምስጋናውና የምርቃቱ ጊዜ መርዘም ከእጥፍ በላይ ሆኖ እንዲሰማኝ አድርጎ ነበር። ይህን እውነት ደግሞ ዳቦ ወዳድ የሆነ ሁሉ ይጋረዋል ብዬ አምናለሁ።

እንደ እስፖንጅ ለስልሶ እንደ ኬክ ማራኪ በነበረው ሸግዬ ዳቦ ሆድ ላይ ቢላዋ አርፎ በቁመቱ መቆረስ እንደጀመረ ደግሞ ሌላ የመብላት ፍላጎትን የሚጨምር ነገር ተፈጠረ። ይህ እንዲሆንም ለጣዕምና ለጥፍጥና ሲባል የተጨማመሩ ቅመማቅመሞች መአዛ በፍጥነት አፍንጫን ለማወድ ሀይል ነበራቸው። አሁን በእጅጉ የጓጓሁለት ድፎ ዳቦ በትልልቁ እየተቆረሰ ለታዳሚው መታደል ጀምሯል።

በወቅቱ እንደኔው ለመብላት የቋመጡትን ጨምሮ ለዳቦ እምብዛም ነን ሲሉ የቆዩ ሳይቀሩ ከፍ ከፍ ካሉት ቁራሾች መካከል የተሻለውን እያማረጡ ሲያነሱ አስተውያለሁ። ሆኖም ግን ለምን? ስል አልታዘብኳቸውም። ጉዳዩ ይህን ለማለት የሚያስችል ግምት እንደማያሰጥ ተረድቻለሁና እኔ ዘንድ በቶሎ ደርሶ በእጄ እስካደርገው ብቻ ተመኘሁ። ዳቦ አዳዩ አጠገቤ እንደደረሰም ከሌሎቹ በማይተናነስ ምርጫ በአቆራረሱ የተሻለ ነው ያልኩትን ወፈር ያለ ዳቦ አነሳሁ።

ለስላሳው፣ ባለ ጥዑም መአዛውና ድንቅ የሆነው ዳቦ ከእጄ እንደገባም ቅርፊቱን ዳርና ዳር ትቼ ሆድ ሆዱን ቡጭቅ ፣ ቡጭቅ አደረግሁት። ይህን ከማድረጌ ጥቂት ዘግይቶ ለአፌ የደረሰው ቃና ግን በእኔ አገላለጽ እጅግ አስደንጋጭ የሚባል ሆነ። የጎረስኩትን ለአፍ ከበድ የሚል ቁራሽ ለመትፋትም ሆነ ለመዋጥ ተቸግሬ በተጨነቅሁበት አፍታ ዞር ብዬ ሌሎችን አስተዋልኩ። ልክ እንደኔ ሁሉ በተመሳሳይ ችግር ውስጥ የነበሩ እንግዶች ሲያዩት ካማራቸውና አሁን ግን ሊተፉትም ሆነ ሊውጡት ከቸገራቸው ዳቦ ጋር ሲተናነቁ ነበር። ከእነሱም መሀል የጎረሱትን ሳይተፉ ወደ ውጭ የሮጡትን አስተውያለሁ። ጥቂት ቆይቶና ሁሉም ተረጋግቶ ግን አብዛኛው ዳቦ ተጋባዥ የራሱን አስተያየት መሰንዘር ጀመረ።

እኔ ዳቦውን ስቀምሰው ቀድሞ ለውስጤ የተሰማው የሽቶ አልያም የሰነደል ጣዕም ነበር። የእኔ ግምት ይህ ቢሆንም ሌሎች ደግሞ የሰንደሉንና የሽቶውን ስም ሳይቀር በመጥቀስ ትክክለኛውን ቃና በማረጋገጫነት የተናገሩ አልጠፉም ። ያም ሆነ ይህ ግን እንዲያ ለመብላት በእጅጉ የጓጓንለት ዳቦ እንዳሰብነው ሆኖ አልተገኘም። እንግዶቻቸውን ለመጋበዝ ሽርጉድ ይሉ የነበሩ ሰዎችን እጀ ሰባራ ያደረገውና ለዳቦው ያልተለመደ ጣዕም መፈጠር ምክንያት የሆነው ደግሞ ዱቄቱ የተገዛበት ስፍራ ከሚሸቱ ነገሮች ንክኪ የራቀ አለመሆኑ ነበር።

ይህን አጋጣሚ ካየሁ በኋላ በአንዳንድ የሸቀጣሸቀጥ ሱቆች ውስጥ ያስተዋልኩት ጉዳይ ደግሞ እንደዳቦው ጣዕም በቀላሉ የሚታለፍ ባለመሆኑ በአሳሳቢነቱ እንዳነሳው አስገድዶኛል። ሁሉም የሸቀጣሸቀጥ መደብሮች ውስጥ ይከሰታል ባይባልም አልፎ አልፎ አንዳንድ ነጋዴዎች ለምግብነት የሚውሉትን ፍጆታዎች መርዝነት ካላቸው ሸቀጦች ጋር በማስቀመጥ ለገበያ ሲያቀርቧቸው ይስተዋላል። አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ ምግብን ከመርዝ ለይቶ አለማኖሩ ዋና ችግር ሆኖ ሳለ «እንጀራ አለ» ከሚለው መጠቆሚያቸው ስር የአይጥ መርዝም እንደሚሸጥ በጉልህ መጻፋቸው ነው።

ጉዳዩን በቀላሉ ላስተዋለው ምንአልባትም ይህ መባሉ ምንም ችግር እንደማይኖረው ሊገምት ይችላል። ይሁን እንጂ በየትኛውም መመዘኛ ለአይጦች መግደያ የሚውል መርዝ ለሰው ልጆች ምግብ ከሆነው እንጀራ ጋር ተዛምዶ ለሽያጭ መዋሉ ተገቢነት አይኖረውም። በተመሳሳይ ሁኔታ የበረሮ ማጥፊያ መድሀኒቶች፣ የትኋንና የቁንጫ መግደያ መርዞች፣ እንዲሁም ለተመሳሳይ አገልግሎት የሚውሉ ተገቢ ያልሆኑ አንዳንድ ሸቀጦች የምግብነት ይዘት ካላቸው ጋር ተቀላቅለው የመቀመጣቸው እውነት በተጠቃሚው ጤንነት ላይ ስጋት ማስከተሉ አይቀሬ ይሆናል።

አሁን አሁን መቅረቱ በጀ እንጂ ቀደም ሲል በአንዳንድ ሱቆች ምንነታቸው ያልተመረመረና ለራስ ምታትና ለመሰል የህመም አይነቶች ይውላሉ የሚባሉ መድሀኒቶች ሳይቀር ለሽያጭ ይቀርቡ እንደነበር ማስታወስ ይቻላል። እነዚህ መድሀኒቶች በእንክብል መልክ የተዘጋጁ ሲሆኑ ማንኛውም ታምሜያለሁ የሚል ጠያቂ እንደማንኛውም ሸቀጥ እየገዛ ሲጠቀምባቸው ቆይቷል። ብዙ ጊዜም በባዶ የቴትራሳይክልና የአምፒስሊን ማሸጊያዎች ውስጥ መድሀኒትነት የሌለውን ነጭ የዳቦ ዱቄት በመተካት ግንዛቤ ባልነበረው ተጠቃሚ ህይወት ላይ ሲቀልዱ ኖረዋል። በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በገንዘቡና በቀላሉ በማይተካው ጤንነቱ ላይም ያልተገባ ትርፍ ሲያጋብሱ የቆዩ እራስ ወዳድ ነጋዴዎች እንደነበሩም መዘንጋት አይቻልም።

ሁሉም ነገር በተገቢው ቦታ ሲገኝና ለተገቢው አገልግሎት ብቻ መዋል ሲችል ወንጀል አይሆንም። ማንኛውንም ዕቃ የመሸጥ ፍላጎት የሁሉም ነጋዴዎች መብት ነው ሊባል ቢችልም መርዝንና ምግብን በአንድ አጎራብቶ «እንካችሁ» ማለት ግን አግባብነት አይኖረውም። ከዚሁ ጎን ለጎንም ቅባትና ሳሙናን፣ ሰንደልና ሽቶን፣ ዘይት፣ጋዝና ወዘተ የመሳሰሉትን አቀራርቦ በማስቀመጥ ለሽያጭ እንዲውሉ ማድረግ አስነዋሪ ተግባር ነው። በተለይ በተለይ የአይጧንና የእንጀራችንን ጉዳይ ጎን ለጎን በማስቀመጥ በሚፈጠር ስህተት በሰዎች ህይወት አደጋ መፍጠር ግን በህግ ሊያስጠይቅ ግድ ነው እላለሁ።

 

መልካምስራ አፈወርቅ

 

 

Published in መዝናኛ

 

የአዲስ ዘመኗ መልካምሥራ አፈወርቅ ዛሬ ስድስት ኪሎ ወደሚገኘው የአንበሶች ጊቢ ትወስደናለች፡፡ ጋዜጠኛዋ በዚያ ጊቢ በተለምዶ ከሚሰሙና ከሚታዩ የአንበሶችና ለሌች የዱር እንስሳት ውሎ ባሻገር ያለውን ህይወት አሁን ለእድሳት ከመዘጋቱ በፊት ታዝባ በማስታወሻዋ የከተበችውን ትነግረናለች፡፡ በአንበሶች ጊቢ ሰዎችና እንስሳት ሳያወሩ ሲግባቡ፤ ሳይነጋገሩ መልዕክት ሲለዋወጡ ለአመታት መኖራቸውንም እንዲህ ስትል ተርካዋለች፡፡

 

ካለሁበት አካባቢ በቅርብ እርቀት የሚሰማውና በጉልህ የሚያስገመግመው የአንበሶች ድምጽ ውስጥን ያሸብራል። ከዚህ በተቃራኒ ጊቢውን በድምቀት የሞላው የአዕዋፍ ዝማሬ ደግሞ ለመንፈስ እርካታን እንደሚሰጥ መሸሸግ አይቻልም። ዝንጀሮዎችና ጦጣዎችን ጨምሮ ከሰላሳ በላይ የዱር እንስሳት በጉርብትና ከሚኖሩበት መንደር በአካል ተገኝቻለሁ፤ ስድስት ኪሎ ባለው የአንበሶች ግቢ፡፡

የጊቢውን በር አልፌ ወደ ውስጥ መዝለቅ ስጀምር ግን መደነቅ አይሉት ፍርሃት ውስጤ እንደነበር አልዘነጋም። እውነት ለመናገር በወቅቱ ከመደነቁ ይበልጥ ያመዘነብኝ ስሜት የበዛ ፍርሃት እንደነበር ቆይቼም ቢሆን ተረድቻለሁ። በወቅቱ የበዛ ፍርሃት ቢሰማኝም ግን እንደማይፈረድብኝ አምናለሁ። ለምን? ካሉ ደግሞ እግሬ የረገጠበት ስፍራ እንዲህ በቀላሉ የሚዳፈሩት አይደለምና ነው።

በብረት አጥሮች ተከበው እንደዋዛ ከማያቸው አንበሶች አጠገብ ብሆንም የእነሱን አንበሳነትና የእኔን ሰው መሆን መዘንጋት ግን ቀላል አልሆነልኝም። ከወዲያ ወዲህ በልበሙሉነት ከሚንጎማለሉት አንበሶች መሀል ጥቂቶቹን በመቃኘት ላይ ነኝ። በመካከላችን ያለው ርቀት አጭር የሚባል ነውና አንበሶቹን ከማንኛውም ንክኪ ለመታደግ ሲባል ከለላ የተደረገውን የብረት አጥር ብቻ ማመኑ ተገቢነቱ አልታየኝም።

አይኖቼን ግራና ቀኝ ማማተሬን ቀጥያለሁ። በአጥሩ ውስጥ ከሚገኙት አስራሁለት አንበሶች መሀል የመጀመሪያው ትኩረቴ ሽማግሌው ላይ ሆነ፡፡ ዘግየት ብሎም የዚህ አንበሳ ስሙ ጠንክር እንደሚባል ተነግሮኛል። ጠንክር ከሀያ አምስት ዓመታት በላይ በጊቢው እንደመኖሩ እርጅና ተጫጭኖታል። በተለይ ሚስቱ አንበሲት ወርቅነሽ በሞት ከተለየችው ወዲህ ሀዘን አይሉት ብቸኝነት ጉልበቱን ነጥቆ ብርታቱን ነፍጎታል። ከአመታት በፊት ያስፈራ የነበረው የጎፈሬው ግርማ ዛሬ ለምልክት ያህል አይታይም። ቆዳው በእጅጉ መሸብሸብ በጀመረው ጠንክር አይኖች ላይ ውር ውር የሚሉትን ዝንቦች ሳስተውል እውነትም አንበሳ ሲያረጅ የዝንብ መጫወቻ ስለመሆኑ አረጋገጥኩ።

በፍርሀት የሚንቀጠቀጠውን እጄን ይዞ መንደሩን የሚያስጎበኘኝ አቶ ምትኩ ጭብሳ ለዓመታት በግቢው መቆየቱ የአንበሶቹን ባህርይና ልማድ ጠንቅቆ እንዲያውቅ አድርጎታል። ምትኩ አንበሶቹንና ሌሎች የዱር እንስሳትን የመጠበቅና የመመገብ ሃላፊነት አለበትና ከሁሉም ጋር የመላመድ ያህል ይተዋወቃል። እሱ እንደሚለው በጊቢው የሚገኙ የዱር እንስሳት እንደመልካቸው ሁሉ ባህርይያቸውም የተለያየ ነው። መሆንና ማድረግ የሚገባቸውንም በራሳቸው ስሜት ይገልጻሉ። በተለይ አንበሶቹን ከልጅነታቸው ጀምሮ በመንከባከብ የማሳደጉ ዕድል ነበረውና ከሰዎች ሁሉ ለይተው እንደሚያውቁት ይናገራል። ካሉት አንበሶች መሀል በሃይለኝነቱ የሚታወቀው ሃይሌ የተባለው አንበሳ ነው።ይህ አንበሳ ስያሜውን የተቸረው በጀግናው አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ ስም ሲሆን ባህርይውም ከሌሎች አንበሶች ለየት ይላል።

ሃይሌ ጎረምሳ እንደመሆኑ ልዩ ጥንካሬና ብርታት ይታይበታል። በቡኒ ጎፈሩና በሃይለኝነቱ የሚለየው ይህ አንበሳ ግዙፍና አስፈሪ የሚባል ነው። ሃይሌ መጋቢዎቹን በፍቅር የመቅረቡን ያህል ለቁጣና ለንዴትም ትንሽ ይበቃዋል። ከልዩ ግርማ ሞገሱ ጋር በሩቁ የሚሰማው ድምጹ ያለው የማሸበር ሃይል የላቀ ነውና በቀላሉ ያስደነግጣል። ምትኩ የዝንጀሮዎቹንና የጦጣዎቹን ፍላጎትንም ጠንቅቆ ያውቃል። እነሱም ቢሆኑ ለሰላምታ የሚጠጉት ሳይቀር የሚተናኮሉት ስለሚመስላቸው ብዙ ጊዜ አስተያየታቸው በጥርጣሬ እንደሆነ ይናገራል። ቀረብ ብለው የሚያወሩ ከተገኙ ደግሞ ከቁጣ በዘለለ ድርጊቱን በጨኸትና በሃይል ለመከላከል ይሞክራሉ።

በተለይ ደጉ የተባለው ጭላዳ ከጎብኚዎች ጋር ያለው ቅርበት ለየት ይላል። ይህ ዝንጀሮ ከሰዎች ብስኩትና ቆሎ መቀበልንም ለምዷል። በቀላሉ የመግባባትና ትኩረት የመሳብ ድርጊት ስላለውም በእሱ ዙሪያ የሚሰበሰቡ ጎብኚዎች ቁጥር በርከት ያለ ነው። ደጉ ጭልፊት ከተባለችው አቻው ጋር በትዳር መኖር ከጀመረ አመታትን ቢያስቆጥርም ጥንድ ሆነው ለሚጎበኙት ባልና ሚስት ግን ፊት መስጠት አይወድም። የመግባባትና የመደሰቱን ያህል እነሱን ሲያይ በእጅጉ ይበሳጫል። ጥርሱን እየነከሰና እየዘለለም ተቃውሞውን ለማሳየት ይሞክራል። በተለይ ጥንዶቹ የሚተቃቀፉ ከሆነ የያዘውን ከመወርወር አይመለስም። መጮህና በቅናት መንጨርጨርም ልማዱ ነው። ምትኩ ይህን ስለሚያውቅ የሁሉንም ፍላጎት አቻችሎ እንደየባህርያቸው ለመያዝ ይሞክራል። ይህ ከአብሮነት ብዛት የመጣ ቅርበትም እንስሳቱንና ተንከባከቢያቸውን በተለያየ ቋንቋ እንዲግባቡ አድርጓቸዋል።

ከግቢው አንድ አቅጣጫ ራቅ ብሎ የሚታየው ቀይ ጦጣ ብቸኛ ነው። ከጊዜያት በፊት በሞት ያጣት ሚስቱና አንድዬ ልጁ ሞት ሀዘንም በእጅጉ የጎዳው ይመስላል። እንደ ጭላዳው ደጉ ድምጹ በርቀትና በጉልህ የማይሰማውን ጦጣ ቀርቤ ለማየት ባልችልም ዝምታውና ብቸኝነቱ ግን ሳያሳዝነኝ አላለፈም።

ከዱር እንስሳቱ መንደር ጉርብትናን ተጋርተው ከሚኖሩት መሀል አንበሲት ልይሽ ተረፈና ባለቤቷ ቃኘው ወርቁ ይገኙበታል። ባልና ሚስቱ ሰላማዊ የሚባሉና መከባበር የሚታይባቸው ናቸው። ብርቅዬና መኮንንም ከአስር አመታት በላይ በትዳር ቆይተዋል። እነዚህ ጥንዶች የትዳራቸው ፍሬ የሆኑ አራት ደቦሎች የነበሯቸው ቢሆንም ሁሉንም በሞት ተነጥቀዋል። መኮንን ቁጡና ግልፈተኛ የሚባል አንበሳ ነው። ባለቤቱ ብርቅዬ ግን ታጋሽ፣ ዝምተኛና ለጸብ የማትቸኩል ቁጥብ እንደሆነች አስጎብኝዬ ምትኩ ይናገራል።

የሽማግሌው ጠንክር ልጅ ወጣቱ ሰሎሞንና ባለቤቱ ሰናይትም በዕድሜ አቻ የሚባሉ ጥንዶች ናቸው። ሰሎሞን ከሀይለኝነት በዘለለ አስቸጋሪ የሚባል ባህርይ መገለጫው ነው። ወይዘሪት መሰረት ደፋር ደግሞ ገና ለትዳር የታጨች ጉብል ናት። ልክ እንደመሰረት ሁሉ እህትማማቾቹ እጅጋየሁና ጥሩነሽ ዲባባም አላገቡም። ትዳር ይዘው የራሳቸውን ጎጆ እስኪቀልሱም በአንድ ቤት ሊኖሩ ግድ ሆኗል።

ከሁሉም ግን ቀነኒሳ የተባለው አንበሳ ሀይለኝነት ከማንም የከፋ ነው። ቀነኒሳ የቀረቡትን በፍቅር ከመቅረብ ይልቅ ሀይልና ጉልበትን መጠቀም ይቀናዋል።እናም እሱ ዘንድ አይደለም መቅረብ በአጠገቡ ለማለፍ እንኳን የሚያሰጋ ነው።ይህ ክፉ ባህርይው ደግሞ ለእንግዶችም ለተንከባካቢዎቹ ፈተና ሆኖ ቆይቷል።

ከሰላሳ ስድስት አመታት በላይ በአንበሳ ግቢ የሰሩት አቶ ተዘጋ ወርቅነህ በየቀኑ ለአንበሶቹ የሚቀርበውን በሬ ለምግብነት ሲያዘጋጁ ቆይተዋል። የእነሱን ጽዳት የመጠበቅ ሀላፊነትና ጤንነታቸውንም ከበሽታ የመከላከል ግዴታም እንዳለባቸው ይናገራሉ። አንበሶቹ የህመም ምልክት ሲኖራቸውና የተለየ ባህሪ ሲያሳዩ በወቅቱ ለሀኪሞች በማሳወቅ አስፈላጊው ምርመራ እንዲካሄድ ያደርጋሉ።

በአንበሶቹ መኖሪያ ዘልቆ በተለየ ሁኔታ መቀራረቡ የማያስደፍር ቢሆንም ጎፈራቸውን እየነካኩና ገላቸውን እየደባበሱ ማጫወቱን ግን ለምደውታል። በሀገራችን ታዋቂ አትሌቶች መጠሪያ የተሰየሙት አንበሶች የራሳቸውን ስም ለይተው ያውቃሉ። ተንከባካቢዎቻቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ ያሳደጓቸው በመሆኑም ምን ቢቆዩና አለባበሳቸውን ቢቀይሩ ማንነታቸው አያጡትም።

እንደ አቶ ተዘጋ አገላለጽ፤ አንበሳን ካለመዱትና እንደ ባህርይው ከያዙት ገራም የሚባል እንስሳ ነው። ደቦሎቹም ቢሆኑ ከተወለዱ ከሁለት ወራት በኋላ መጥባታቸውን አቁመው ስጋ ስለሚመገቡ ከአሳዳጊዎቻቸው ጋር የሚኖራቸው ቅርበት የጠበቀ ይሆናል። ወንዱ አንበሳ ቀን ውጭ ውሎ ማታ ወደ ጎጆው ሲዘልቅ ለቤተሰቡ ያለውን ፍቅር የሚገልጸው ልጆቹንና ሚስቱን በማቀፍና በተለየ ሁኔታ በመንከባከብ መሆኑን ይናገራሉ። ይህ እውነታ ደግሞ «ፍቅርና መተሳሳብ ያለው በሰው ልጆች ብቻ መሆኑን ለምናስብ ሁሉ ስህተት መሆኑን ትልቅ ማሳያ ነው» ይላሉ አንጋፋው የአንበሶች ተንከባካቢ ተዘጋ ወርቅነህ።

በመዲናችን አዲስ አበባ ብቸኛ የሆነው የአንበሳ ግቢ ከተመሰረተ ስልሳ ስምንት አመታትን አስቆጥሯል። በዚህ ጊቢም ስመጥሩውን አንበሳ ሞላን ጨምሮ ሌሎች አንበሶችና የተለያዩ የዱር እንስሳት በአንድነት ሲኖሩ ቆይተዋል።የዱር እንስሳት ባህርይና የአኗኗር ልምድ ከሰው ልጆችና ከቤት እንስሳት የተለየ በመሆኑ ሲርባቸው ለመመገብ፣ ሲያማቸውም ህክምና ለመስጠት ልዩ ጥንቃቄና ዘዴን ይጠይቃል።

ዶክተር ዮሀንስ ተሰማ በጊቢው የዱር እንስሳት ሀኪም በመሆን ይሰራሉ። እሳቸው እንደሚሉት የዱር እንስሳቱን ለማከም ከሚመገቡት ምግብና ከሚጠጡት ውሃ ጋር በማዋሀድ በተለያዩ ዘዴዎች መድሃኒት እንዲሰጣቸው ይደረጋል።የዱር እንስሳቱ መድሃኒት በሀገር ውስጥ የማይገኝ በመሆኑም ከሚመለከታቸው ሀገራት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ህክምናው ይካሄዳል። ለዱር እንስሳቱ ህክምና አሰጣጥ አሁን ያለው ቦታ አመቺ ነው ባይባልም አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ መታከም የሚኖርባቸው እንስሳት ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ በመደረግ ላይ ነው።

እንደ ዶክተር ዮሀንስ አገላለጽ በግቢው ከህክምና ጉድለት ጋር ተያይዞ እስካሁን ያጋጠመ ችግር የለም። ይሁን እንጂ በዕድሜ መግፋት ሳቢያ አምናና ዘንድሮ ሁለት አንበሶች ሞተዋል። ሆኖም አንዳንድ ጎብኚዎች እንስሳት የማይመገቧቸውን ምግብ ስለሚሰጡና ቦታውም ከሰዎች ንክኪ የተከለለ ባለመሆኑ እስካሁን አንድ ሚዳቋና አምባራይሌ ሊሞቱ ችለዋል።

1940 .ም ጀምሮ ሶስተኛ ትውልድ በመሆን በመራባት ላይ የሚገኙት አንበሶች እንደቤተሰባቸውና ዝርያቸው አይነት ተለይተው የሚኖሩበት ሁኔታ እንዳለ ዶክተር ዮሀንስ ይናገራሉ። ከአቅም በላይ ሊፈጠር የሚችለውን የመራባት ሂደት ለመታደግም የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሃኒቶችን መጠቀም ግድ ይላል። በሰው ልጆች ላይ የሚያጋጥሙ ተመሳሳይ የጤና ችግሮችን እንስሳትም የመጋራት ባህርይ እንዳላቸው የሚናገሩት ዶክተር ዮሀንስ፤ ይህ አይነቱ እውነት ብርቅዬ በተባለችው አንበሳ ላይ የመከሰቱን ሂደት እንደማሳያ ይጠቅሳሉ። ደጉ የተባለው ጭላዳ ዝንጀሮም የሚታይበት ቀናተኛነትና ንዴትም ከሰዎች ማንነት ጋር ተመሳሳይ ነው።

ዶክተር ሙሴ ክፍሎም በግንባታ ላይ ያለው የአዲሱ የዱር እንስሳት ፓርክ ስራ አስኪያጅ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉትም ስድስት ኪሎ የሚገኘውና በተለምዶ አንበሳ ግቢ በመባል የሚጠራው የዱር እንስሳት ማቆያ እንደ ዕድሜው አንጋፋነት ደረጃውን የመጠነ አገልግሎት እየሰጠ አልነበረም። በአሁኑ ጊዜ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ ፓርክን መገንባት አስፈላጊ በመሆኑ በአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ስራው በመከናወን ላይ ይገኛል። ግንባታው ተጠናቆ ስራ ሲጀምርም እስካሁን ለአመታት መልስ ያልነበራቸውና በግቢው ውስጥ ይታዩ የነበሩ ችግሮች ሁሉ መፍትሄ ያኛሉ። ጊቢው በአገልግሎት ብዛት ጥገናና ለውጥ የሚያስፈልገው መሆኑ ስለታመነበትም ከመስከረም 21 ቀን 2009 .ም ጀምሮ የጎብኚዎች አገልግሎት ተቋርጦ ስድስቱ አንበሶችና ሌሎች እንስሳት ወደ አዲሱ ፓርክ ተዛውረው እንዲቆዩ ተደርጓል።

የዓመታት ጉዞ ያጀበው የተለያየ ማንነት፣ የማይመሳሰል ቋንቋና ኑሮ እነሆ በአንድ ግቢ ህይወትን አጣምሮ አብሮነትን ሊቀጥል ግድ ሆኗል። ይህ ማንነት ያልገደበው ወዳጅነት አናብስቶችና የሰው ልጆች ባለመግባባት እንዲግባቡ፣ ባለመተዋወቅ እንዲተዋወቁ፤ በመፈራራትም ሆነ በመቀራረብ አብረው እንዲቀጥሉ ይህ የህይወት መንገድ እንዲህ አገናኝቷቸዋል።

 

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

   

አቶ ግርማ ባልቻ፤                                         ተባባሪ-ፕሮፌሰር-ያዕቆብ-አርሳኖ፤                አቶ ካህሳይ ገብረእየሱስ

 

ሰሞኑን ከወደ ግብፅና ደቡብ ሱዳን በመገናኛ ብዙኃን ሲናፈሱ የነበሩ ዘገባዎች ይዘት በኢትዮጵያ ጎን ሆኖ ለተመለከታቸው አስገራሚም ብቻ ሳይሆን አስደንጋጭም ነበሩ፡፡ ዘገባዎቹ ደቡብ ሱዳንና ግብፅ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ ስምምነት ስለማ ድረጋቸው የሚገልጹ ናቸው፡፡ በእርግጥም የተባለው እውነት ከሆነ የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳንን ግንኙነትን የሚያሻክርና "የሰይጣን ጆሮ አይስማ" የሚያስብል ነው። በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደርና የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ልዩ አማካሪ በግብፅና በሱዳን መካከል የተደረገው ስምምነት ግን ኢትዮጵያን እንደማይጎዳ ይፋ አድርገዋል፡፡ ለአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ አዲስ አበባ የሚገኙት የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንትም ይሄንኑ ደግመውታል።

የደቡብ ሱዳንና ግብፅ ወዳጅነት አንድምታ

አቶ ግርማ ባልቻ በግብፅ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ሆነው አገራቸውን አገልግለዋል፡፡ እርሳቸው እንደሚሉትም፤ የግብፅና የደቡብ ሱዳን ግንኙነት መሰረቱ ጤናማ አይደለም።ምክንያታቸውም ግብፅ ከሱዳን በላይ የደቡብ ሱዳንን ነፃነትን ስትቃወም የቆየች አገር መሆኗ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በባላንጣነት የሚተያዩና የሻከረ ግንኙነት የነበራቸው አገራት መሆናቸውም የሚጠቀስ ነው። አሁን ግን ከዚያ በተቃራኒ አንዳንድ ነገሮች እየታዩ ነው።

እኤእ በ2014 የቀድሞው ግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደቡብ ሱዳንን ጎብኝተው ነበር።የአሁኑም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁ በደቡብ ሱዳን ጉብኝት አካሂደዋል። በተመሳሳይ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቨኪርም እንዲሁ በ2014 ግብፅን ጎብኝተዋል። ሰሞኑንም ወደ ግብፅ በመሄድ ስምምነት አድርገዋል። እነዚህ ጉብኝቶች ደቡብ ሱዳንን ከናይል ኢንሸቲቪ የትብብር ስምምነት በመነጠል ከግብፅ ጎን ለመሰለፍ እንዲሁም የጋራ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚደረጉ ጥረቶች ማሳያ ናቸው የሚል እምነት በአቶ ግርማ ዘንድ አለ።

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የነበራቸው ጠንካራ ግንኙነት የቆየ በመሆኑ ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያን ለመጉዳት የሚያበቃት ምክንያት የላትም ብለው እንደሚያምኑ አቶ ግርማ ገልፀው፤ በአንፃሩ ግብፅ ላይ ግን ጥርጣሬ እንዳላቸው ነው የሚናገሩት፡፡ "በተለይ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ የተከናወኑትን ጉዳዮች መመልከት ብቻ በቂ ይሆናል፡፡ የኤርትራው መሪ ግብፅን ጎብኝተዋል። የግብፁ መሪ አልስሲ ሩዋንዳን ጎብኝተዋል። የኡጋንዳ፣ የጂቡቲውንና የደቡብ ሱዳን መሪዎችንም ጠርተው አነጋግረዋል። ይህም ኢትዮጵያን የማካለብ የሚመስሉ ነገሮች አሉት። የተደራጀና ትርጉም ያለውም ጉብኝት ይመስላል። ስለሆነም ጉዳዩን በጥንቃቄ መመልከት ይገባል" ባይ ናቸው አቶ ግርማ።

እንደ ዲፕሎማቱ ገለጻም፤ ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያን የሚጎዳ ተግባርና ስምምነት ካደረገች ችግር ውስጥ የምትወድቀው እራሷው ነች። ስለዚህ ደቡብ ሱዳን ከግብፅ ጋር ያደረገችው ስምምነት ኢትዮጵያን የሚጉዳ ነው ብሎ መውሰድ አስቸጋሪ ነው። የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ግንኙነት እየሻከረ መጥቷል ለማለት የሚያስችሉ ነገሮች ስለመኖራቸው ምንም ፍንጭ የለም፡፡ ስለሆነም ግብፅና ደቡብ ሱዳን ተሻርከው ኢትዮጵያን ሊያጠቁ ነው የሚል ድምዳሜም መያዝ አስቸጋሪ ነው።

በአንፃሩ የሁለቱ አገራት አፍላ ፍቅር ከኢትዮጵያ ይልቅ ሱዳንን ለመጉዳት የታሰበ ይመስላል ባይ ናቸው። ምክንያታቸውን ሲገልፁም ሱዳን በህዳሴው ግድብ ላይ ከኢትዮጵያ ጎን መሰለፏ ግብፅን አለማስደሰቱ ነው። በዚህና በሌሎች ጉዳዮች የተነሳ በግብፅ አስተባባሪነት ኡጋንዳ፣ ግብፅና ደቡብ ሱዳን ሆነው ሱዳንን ለማጥቃት የፈጠሩት ህብረትና እንቅስቃሴ ስለመኖሩ ፍንጮቹ ጎልተው እየታዩ ናቸው።

"ደቡብ ሱዳን ጠንካራ መንግስት በሌለበት ሁኔታ ከኢትዮጵያ ጋር የተካረረ ግንኙነት ይገባሉ የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም ተፅእኖው እነሱ ላይ ነው የሚበረታው። በአንፃሩ ከሱዳን ጋር የድንበር ግጭት አላቸው። በሰላም ድርድር አርግበውት እንጂ ጦርነት ሊገቡ የነበሩ አገሮች ናቸው። የግብፅ አላማ ደግሞ ደቡብ ሱዳንን ሆነ ሱዳንን ከኢትዮጵያ በመነጠል ተፅእኖ መፍጠር ነው። በተለይ ሱዳን ውስጥ ደካማ መንግስት በመፍጠር ፖለቲካዊ ተፅእኖ ማሳደር ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይችላሉ ብዬ ነው የማስበው። ኡጋንዳ እኤእ በ2010 የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን ፈርማለች። ነገር ግን ኡጋንዳ በፓርላማዋ እንዳታፀድቀውና ህግ ሆኖ እንዳይወጣ ደቡብ ሱዳን ደግሞ አባል ሆና ገብታ ሌላ ችግር እንዳትሆንባቸው ግንኙነታቸውን በማጥበቅ ደቡብ ሱዳንን በእነሱ ስር በማድረግ መጠቀሚያ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ተግባራቸው ይመስክራል" ነው ያሉት አቶ ግርማ።

በተጠቀሱትና በሌሎች ብዙ ምክንያቶች የተነሳ የደቡብ ሱዳንና የግብፅ ስምምነት ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነው ብለው ለማመን እንደሚቸገሩ ዲፕሎማቱ ይናገራሉ። ምክንያቱም ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ሰፊ ግዛት የምትዋሰን ብቻ ሳይሆን የቆየች ወዳች አገር ናት።ገለልተኛዋ አገር ኢትዮጵያ ናት ተብላም በሁለቱ ሱዳኖች በመመረጧ የኢትዮጵያ ጦር ሰላም አስከባሪ ኃይል ሆኖ ተሰማርቷል። ትንሽ መጎራበጦች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን በዚህ ደረጃ የሚያበቃ የሁለቱ አገሮች ችግሮች እንደሌሉ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል ነው የሚሉት።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰርና ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ በበኩላቸው፤ ደቡብ ሱዳን አዲስ አገር እንደመሆኗ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ከጎረቤቶቿም ሆነ ከሌሎች አገሮች ጋር መገናኘቷ ትክክል ነው ይሉና፤ ይህ ደግሞ የአንድ አገር የዲፕሎማሲ ባህሪ ስለሆነ የሰሞኑ እንቅስቃሴም በዚህ አግባብ መታየት አለበት የሚል አመለካከት አላቸው፡፡

ደቡብ ሱዳን ከግብፅ ጋር ይበልጥ እየተቀራረበች እንደሆነ አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እየዘገቡ ይገኛሉ። የደቡብ ሱዳን መሪም ግብፅ ሄደው ከግብፅ መሪ ጋር መምከራቸውን ሰምተናል። የሁለቱ አገሮች በመሪዎች ደረጃ መገናኘት በራሱ ችግር ባይሆንም በኢትዮጵያ ላይ ጫና የሚፈጥረው የኢትዮጵያን ጥቅም በሚጎዳ መንገድ ስምምነት ካደረጉ ብቻ ነው የሚል አመለካከትም አላቸው። ነገር ግን ደቡብ ሱዳን በሯሷ ጉዳይ ግንኙነት ብታደርግ ማንንም ሊያስጨንቅ አይገባውም። ምክንያቱም መንግስታት ከሌሎች መንግስታት ጋር ይገናኛሉና።

የደቡብ ሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስትር «ደቡብ ሱዳን ጥቅሟን ለማስከበር ኢትዮጵያን አትፈራም» ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል። ይህ ንግግር ምን አድምታ ይኖረዋል? የአዲስ ዘመን ጥያቄ ነበር፤ "ዘገባው ዝርዝር ጉዳይ ስሌለው በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር ትንታኔ መስጠት ያስቸግራል። ሆኖም ደቡብ ሱዳን የራሷን ጉዳይ በምትፈፀምበት ጊዜ ሌላው ወገን ለምን እንደዚህ ታደርጊያለሽ ብሎ አስተያየት ከሰጠ ምን አገባችሁ ማለታቸው አይቀርም። ስለሆነም የደቡብ ሱዳን ማስታወቂያ ሚኒስትር ይህንን ማለት የቻሉት በደቡብ ሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት በሶስተኛ ወገን የተነሳ እየሻከረ ከሄደ እኛ ጥቅማችን ለማስከበር መብታችን ነው ለማለት የተናገሩት ይመስላል" የሚለው ደግሞ የዶክተር ያዕቆብ ምላሽ ነው።

ዶክተር ያዕቆብ እንዳሉትም፤ ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን የተነሳውን የእርስ በእርስ ችግር ስትሸመግል እንደቆየች ይታወቃል። እንደገና ባገረሸው ችግርም የሪክ ማቻር ኃይል ከፕሪዚዳንቱ ጋር ተቃርኖ ስላላቸው ሁለቱን ወገኖች በማስታረቅ ወደ ሰላም ለማምጣት ኢትዮጵያ ያደረገችው ጥረት መጥፎ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ነገር ግን እያንዳንዱ ተቀናቃኝ ወገን ሲታረቅም ሲጣላም ሰበቡን በሌላ ወገን ላይ ሊያደርግ ይችላል። የሆነው ሆኖ የግብፅና የደቡብ ሱዳን ስምምነት በደንብ ተጣርቶ ስላልወጣ ጫፍ ጫፉ በመገናኛ ብዙኃን ስለሚወጣ ብቻ ድምዳሜ ለመድረስ አደጋች ይሆናል።

"ግብፅ ደቡብ ሱዳንን በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ትሞክራለች የሚሉ ወገኖች አሉ በዚህ ዙሪያ ምን አስተያየት አልዎት? «ደቡብ ሱዳን ነፃ ከወጣች ጀምሮ ግብፅ በደቡብ ሱዳን ኤምባሲ ከፍታለች። የተራድኦ ሰራተኞች አሏት። በውሃ ጉድጓድም ስትሰራ ቆይታለች። ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላቸውን ጥቅምና ግንኙነት ሲያጠናክሩ እንደቆዩ የሚታወቅ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ግብፅ ደቡብ ሱዳንን ይዛ ኢትዮጵያን ልታጠቃ ነው የሚያስብል አይመስለኝም። ደቡብ ሱዳን የራሷን ጥቅም ለማስከበር ከጎረቤትም ሆነ ከሌሎች አገሮች ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ታካሂዳለች። ስለዚህ ከኢትዮጵያ ባላንጣ አገር ጋር ስለተገናኘች ብቻ ኢትዮጵያን ይጎዳል ብሎ መናገር ችኮላ ነው። ለወደፊቱ ግን ደቡብ ሱዳንም ሆኑ ሌሎች አገሮች ከኢትዮጵያን ጥቅም ጋር ከሚቃረን አገር ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነትና ስምምነት እየተከታተሉ መነጋገሩ ጥሩ መፍትሄ ያመጣል የሚል እምነት አለኝ" የዶክተር ያዕቆብ መቋጫ ነው።

የደቡብ ሱዳንን መንግስት ለረጅም ጊዜ በማማከር የሰሩትና በግጭትና ግጭት አፈታት ዙሪያ ጥናት የሚያደርጉት አቶ ካህሳይ ገብረእየሱስ፤ የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ግንኙነት አገር ከሆነች በኋላ የተፈጠረ ሳይሆን ከአማፂዎቹና ከህዝቦቹ ጋር ቆየት ያለና ጥልቅ ግንኙነት እንደነበራቸው ያስታውሳሉ። የኢትዮጵያ መንግስት ደቡብ ሱዳን አገር ከመሆኗ በፊት በሱዳን የነበረውን ችግር የደቡብ ሱዳን ህዝቦችን የዴሞክራሲ መብት ጥያቄዎች በሚፈታ መልኩ ብርቱ ጥረት አድርጓል። እልህ አስጨራሽ ድርድር ተካሂዶ በህዝበ ውሳኔ ችግሩን መፍታትም ተችሏል። ይህም ለአካባቢያዊ ሰላምና መረጋጋት አስፈላጊ ነበር።

«እኔ የቅርቡን የደቡብ ሱዳንና የግብፅ ግንኙነትንና ውይይትን ብቻ አይቼ አስተያየት ባልሰጥ እመርጣለሁ፡፡ ደቡብ ሱዳን ካለ ህገ መንግስትና የተዋቀረ መንግስት የምትመራ አገር ናት። አሁን ባለው ሁኔታ ሁለቱም ደቡብ ሱዳን ኃይሎች ከኢትዮጵያም ሆነ ከሌሎች አገሮች ጋራ ያላቸው ግንኙነት ስልጣን ላይ ላለው አካል ምን ያህል ጥቅም ይሰጠዋል ከሚል ስሌት በስተቀር ቋሚ የሆነ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲም ይሁን የፖለቲካ ሥርዓት የላቸውም። በዚህ ምክንያትም ከአገሮች ጋር የሚመሰርቱት ግንኙነት ከግለሰብ ቅርርብ ከመሆን ውጪ በሥርዓት የተመራ አይደለም። ገሚሶቹ ከካርቱም መንግስት ከፊሎቹ ደግሞ ከኡጋንዳ ዕርዳታና ድጋፍ ያገኛሉ» የአቶ ካህሳይ አረዳድ ነው።

አቶ ካህሳይ በግብፅ ጉዳይ ላይ ከአቶ ግርማና ከዶክተር ያዕቆብ የተለየ ሀሳብ አላቸው።የግብፅ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ብሄራዊ ጥቅምና በአካባቢው ያለውን ተፅእኖ ለመጠበቅ ወይንም ለማደስ የተሻለ አማራጩ አድርጎ የሚያየው ደቡብ ሱዳንን ነው ይላሉ።ምክንያቱ ደግሞ የተረጋጋና የተጠናከረ መንግስት ስለሌለ ደቡብ ሱዳን መግባት ከቻሉ መንግስት ሊቆጣጠረው በማይችል አካባቢ ኢትዮጵያን ለማተራመስ እድል ያገኛሉ፡፡ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴም ከዚህ ውጪ የሚታይ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ሁለቱን አገሮች ሊያስተሳስር የሚችል የጥቅም ግንኙነት የላቸውም። ማስረጃቸው ደግሞ የናይልን ወንዝ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ ከሚያደርገው ስምምነት የሚጠቀሙት ደቡብ ሱዳኖች ናቸው።

እንደ አቶ ካህሳይ እምነት፤ የግብፅ መንግስት ደቡብ ሱዳኖችን በስምምነቱ እንዳይጠቀሙ ከልክሎ እነሱ ጋር መዛመድ አይችልም። ሆኖም ቡድኖቹን በማታለል የራሱን ስራ መስራት ይፈልጋል። ይህ ስራ መስራት የጀመረውም የደቡብ ሱዳን ጦርነት ከመነሳቱ (ከአምስት ዓመት) በፊት ነው። በፀጥታና በወታደራዊ ስልጠና እንዲረዳዱ ጥያቄ አቅርበው ቦታው ወደ ኢትዮጵያ ደንበር የሚጠጋ በመሆኑ በጊዜው የነበሩ የደቡብ ሱዳን መሪዎች አይሆንም የሚል ምላሽ ሰጥተዋቸዋል። የናይል ጉዳይ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የደቡብ ሱዳንም ጥቅም ነው በሚል ፊት ነስተዋቸዋል። ጦርነቱ ከተነሳ በኋላ ግን የዶክተር ሪክ ማቻር ኃይል በካርቱም ይረዳ ስለነበር የደቡብ ሱዳን የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ወታደራዊ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ከግብፅ ጋር ግንኙነት ጀምረዋል። ከአሁን ቀደምም ግብፆች በወታደራዊ ስልጠና ስም የተወሰነ ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል። ጁባ ውስጥ የግብፅና የኤርትራ ጄኔራሎች ሲቪል ለብሰው ይኖራሉ። ምን ያደርጋሉ? ዓላማቸው ምንድነው? የሚለውን የሚያውቅ የለም። ግብፅም ከደቡብ ሱዳን ጋር የተወዳጀችው ኢኮኖሚያዊ ጥቅሟን ከማስጠበቅ ይልቅ ኢትዮጵያ ላይ ያላትን ጥቅም ለማስፈፀም ነው፡፡

የደቡብ ሱዳን ተቃራኒ ኃይሎች መርህ ላይ የተመሰረተ አቋም ስለሌላቸው ከግብፅ የሚያገኙት ጥቅም ካላቸው ይህን ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ከግብፆች ጋር መወዳጀታቸው አይቀርም። ለዚህም ነው ሳልቫኪር ግብፅ ከመሄዳቸው በፊት በመከላከያ ሚኒስትሩ የሚመራ ልዑክ ወደ ግብፅ አምርቶ የነበረው። ያም ሆኖ ግን ይህንን ግንኙነት ኢትዮጵያን በግብፅ የመተካት ዓላማ ያለው ነው ብሎ መውሰድ ከባድ ነው። ምክንያቱም ከኢትዮጵያ በላይ ግብፆች እንደማይጠቅሟቸው ደቡብ ሱዳኖች ያውቃሉና።

"ሁለተኛው ነጥብ አሁን ያለው የደቡብ ሱዳን መንግስት ግብፆችን መሳሪያ በማድረግ ኢትዮጵያን ማስፈራራት ፍላጎታቸው ነው። ኢትዮጵያ በጠንካራ አቋም የሳልቫኪርን መንግስት እንድትደግፍ ለማድረግና ሌሎች ተቃዋሚዎችን አላውቃችሁም እንድትል የማድረግ አንዱ ስልት አድርገው እየተጠቀሙበትም ይመስለኛል። ስለዚህ የደቡብ ሱዳንና የግብፅ ወዳጅነት ተመልክተን በደቡብ ሱዳን በኩል ያለውን ዝንባሌ ስንገልጠው፤ ኢትዮጵያን ለማስፈራራትና ጥቅሟን ለመቀራመት ካለ ፍላጎት የመነጨ ነው። ስለሆነም «ያልጠረጠረ ተመነጠረ» በሚል መመልከቱ ይበጃል። ለዚህ ማስረጃቸውም ግብፆች ደቡብ ሱዳንን በመጠቀም ኢትዮጵያ ውስጥ የጋለ ወንበር በመትከል ተረጋግተን እንዳንቀመጥበት ለማድረግ እንደሚሰሩ ጥርጥር የለውም" ባይ ናቸው።

ለኢትዮጵያ ረጅም የድንበር አዋሳኟ ደቡብ ሱዳን ናት። በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች ጠንካራ ግንኙነት ፈጥረው የሚኖሩ አይደሉም። የመሰረተ ልማት ችግር ያለበትም አካባቢ ነው።ለወታደራዊ ሆነ ለሌላ እንቅስቃሴ እንደልብ የሚወጣበትና የሚገባበት አይደለም። በእነዚህ መሰረታዊ ምክንያቶችና በግብፅ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ለኢትዮጵያ የስጋት ቀጣና መሆኑ አይቀርም የሚል እምነት በአቶ ካህሳይ ዘንድ አለ። ግብፆች ደግሞ ለዚህ ቅርብ በሆነ አካባቢ ከድሮም ጀምሮ ወታደራዊ ካምፕ የመመስረት ፍላጎት እንዳላቸው መዘንጋት የለበትም ሲሉም ያሳስባሉ፡፡

ደቡብ ሱዳን ወደ ግብፅ ማዘንበሏ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስራ ድክመት መንስኤ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው? ብለናቸው አቶ ካህሳይ ሲመልሱ፤ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ደቡብ ሱዳን ወደ ግብፅ በማጋደሏ ብቻ አይገለፅም።ምክንያቱም የግንኙነቱ አንድምታ ነው መመዘን ያለበት። መነሻና መድረሻው ካልታወቀ በስተቀር እዚህ ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም። ነገር ግን የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከደቡብ ሱዳን አንፃር ሲመዘን ግን ደካማ ነው ማለት እችላለሁ። በደቡብ ሱዳን ያሉ ችግሮችን እስካሁን ድረስ መፍታት አለመቻላችን፣ ከሳልቫኪር መንግስት ጋር የፀና ወዳጅነት ልንፈጥር አለመቻላችንና እኛን በሚያምኑ እኛጋ በሚወግኑ ህዝቦች ላይ የዲፕሎማሲ ስራ በመስራት ለመልካም ነገር ስላላዋልነው ደቡብ ሱዳን ያለንን ጥቅም ሊያስጠብቅልን አልቻለም ብለዋል።

ቀጣይ የዲፕሎማሲ ስራ

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳንን የሚያገናኛቸው ነገሮች ብዙ ናቸው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ከሁሉም አገሮች ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን አጠናክራ መቀጠል አለባት። ከደቡብ ሱዳን ጋር መቃቃር ካለ ደግሞ በመነጋገር ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋል። ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ማጠናከር፤ አሁን ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላትን አይነት ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከደቡብ ሱዳንም ጋር ሊኖር ይገባል። ደቡብ ሱዳን ወደ ናይል ኢንሸቲቭ እንድትገባና ስምምነቱን እንድትፈርም ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል የሚለው የአቶ ግርማ ባልቻ ምክረ ሀሳብ ነው።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮችና ከግብፅም ሆነ ከሱዳን ጋር በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ጥሩ ግንኙነት ለመመስረት ቆርጣ የተነሳች አገር ስለሆነች ይህን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚጠናከርበትን እንጂ የሚላላበትን መንገድ መከተል የለባትም የሚለው ደግሞ የዶክተር ያዕቆብ ሀሳብ ነው።

አቶ ካህሳይ ደግሞ፤ የተጀመሩትን የልማት፣ የዴሞክራሲና የፍትህ ሥርዓት የማስፈን ስራዎች ድንበር አካባቢ ባሉ ህዝቦች አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል ባይ ናቸው። በተለይ ኢትዮጵያም ሆነ ደቡብ ሱዳን ውስጥ ያሉትን የኑዌር ብሄሮችን በኢኮኖሚው፣ በመሰረተ ልማቱና በማህበራዊ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተደረገ ድንበር ዘለል አዎንታዊ ተፅእኖ መፍጠር ይቻላል። ደቡብ ሱዳን ያሉት ህዝቦች ለኢትዮጵያ ደህንነት የሚጨነቁና የሚሰሩ ማድረግ የሚቻልበት ዕድልም አለ። ስለዚህ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባዋል። ሌላው ደቡብ ሱዳን ያሉ የተለያዩ ኃይሎች በአንድነት ተስማምተው ጠንካራ መንግስት እንዲፈጥሩ በኢጋድ በኩል ከሚደረገው ጥረት ባሻገር ኢትዮጵያ በራሷ ጠንካራ ስራ መስራት ይኖርባታል በማለት ሰፊ ስራ እንደሚጠብቃት ሀሳባቸው ገልፀዋል።

 

ጌትነት ምህረቴ

 

 

Published in ፖለቲካ

 

..አ ከ1980ዎቹ ጀምሮ በዓለማችን እየገነነ የመጣው የኒዮ-ሊብራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ፤ መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖረውን ድርሻ የሚገድብ፣ በአንፃሩ የግል ባለሀብቶች የኢኮኖሚ ድርሻን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ አቅጣጫን የሚከተል አካሄድ ተደርጐ ሊወሰድ የሚችል ፍልስፍና ነው። በዚህም መሠረት በተለይ የሦስተኛው ዓለም አገራት በከፍተኛ ደረጃ በይዞታቸው ሥር የሚገኙ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን በሽያጭ ግዙፍ ለሆኑ ዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ኮርፖሬሽኖች እንዲቸበቸቡ በማድረግ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በውጭ ኃይሎ እጅ ሥር እንዲወድቅ ምክንያት ሆኖ አልፏል። ኢኮኖሚያዊ ነፃነት የሌለው መንግሥት የፖለቲካ ነፃነትም እንዲያጣ ስለሚገደድ የአገር ሉአላዊነት እየተሸረሸረ፣ ዘመናዊ እጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ሥር መውደቅን አስከትሏል ማለት ይቻላል።

በኢትዮጵያ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኙ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ የማዘዋወሩ ተግባር ከ1984 ጀምሮ መከናወን ጀምሯል፡፡ በዚህም በአመዛኙ በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበሩ በርካታ ድርጅቶች ከመንግሥት እጅ እየወጡ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች ሥር እንዲተዳደሩ ተደርጓል፡፡ ሂደቱም ውጤታማና ትክክለኛ እርምጃ እንደነበር መረዳት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በመዋላቸው ብቻ ምርታማነትን እና ትርፋማነትን አጥተው በኪሣራ ውስጥ ወድቀው የቆዩ ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታ ከተዘዋወሩ በኋላ አትራፊ ሆነዋል፤ የአገሪቱ ኢኮኖሚም እንዲነቃቃ እድል ሰጥተዋል።

በሌላ በኩል ይህ የመንግሥት እርምጃ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ሲደርስበት የነበረውን የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን በሙሉ ለሽያጭ እንዲያቀርብ የሚያስገድድ ግፊት ያረገበ ሆኗል፡፡ መንግስት ይሄንን ጫናና ግፊት ተቋቁሞ የተወሰኑና የተመረጡት ላይ ብቻ አተኩሮ ተንቀሳቅሷል፤ የፖሊሲ እርምጃውንም ትክክለኛ አድርጎታል፡፡ መንግስት ስትራቴጂካዊ የሆኑትን ተቋማት ማለትም የባንክ፤ የኢንሹራንስ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት፣ ቴሌኮምዩኒኬሽንን እና የኢትዮጵያ መብራት ኃይልን የመሳሰሉ ወሳኝ ተቋማትን በይዞታው ሥር አቆይቷቸዋል፡፡ በዚህም የአገሪቱ ጥቅም የሚከበርበትን ሁኔታ መፍጠር ችሏል።

አሁን አሁን ይህ የመንግሥት አካሄድ እስከምን ደረጃ በዚህ መልኩ ይቀጥላል፤ የትኞቹን ተቋማትንስ ወደፊት ለሽያጭ ያወጣል? የትኞቹን ይዞ ይቀጥላል? የሚለው የወቅቱ አጀንዳ ሆኖ በመውጣት ላይ ያለበት ምዕራፍ ላይ የደረሰን ይመስላል። ለዚህ ምክንያት የሆነኝ በቅርቡ መንግሥት የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅትን (ይህ የቀድሞው መጠሪያው ነው) በከፊል ወደ ግል ይዞታ ለማዞር በማቀድ ከቻይና ኩባንያዎች ጋር ድርድር የመጀመሩ ዜና በመገናኛ ብዙኃን እየተደመጠ የመገኘቱ ጉዳይ ነው።

በመሠረቱ ይህን መሰል የፖሊሲ እርምጃ ሲወሰድ ግልፅነት እና አሳታፊ መሆን ይገባዋል የሚል አስተያየት በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ዘንድ አለ። የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃን ይህን መሰል ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፍ መድረክ መፍጠር ሃሣቦች በስፋት እንዲንሸራሸሩ ማድረግ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ፖሊሲ አውጪዎች የተለያዩ አማራጮችን እንዲያገናዝቡ እድል ይሰጣቸዋልና ነው።

በመሆኑም የትኞቹ ተቋማት ወደ ግል ይዞታ መዘዋወር ይኖርባቸዋል፤ እንደዚሀም ምን ዓይነት መንገድ እና ዘዴ በመጠቀም አገሪቱ የተሻለና አዋጪ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርባታል በሚሉ ሃሣቦች ዙሪያ የተወሰኑ ነጥቦችን በማቅረብ ኃላፊነቴን ለመወጣት ልሞክር። በመጀመሪያ ደረጃ ሁሉንም በመንግሥት ሥር የሚገኙ ድርጅቶችን ለሸያጭ ማቅረብ፤ ወይም በመንግሥት እጅ ሥር የሚገኙ የልማት ድርጅቶችን በሙሉ በመንግሥት ይዞታ ሥር መቆየት አለባቸው የሚሉ ፅንፍ የረገጡ ሃሣቦችን የማልጋራ መሆኑን ለማሳወቅ እወዳለሁ። ሁለተኛ ይህ ከመንግሥት ወደ ግል ይዞታ የማስተላለፉ ጉዳይ በምን መልኩ እና ለእነማን መተላለፍ አለበት በሚለው ነጥብ ዙሪያም እንደዚሁ የዚህ ጽሑፍ የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዞር ጉዳይ ከተለያዩ ምክንያቶች አንፃር የማይቀር ይመስላል፤ ከእነዚህም መካከል ኢትዮጵያ በቅርቡ የዓለም ንግድ ድርጅትን (WTO) የምትቀላቀል የመሆኗ ጉዳይ፤ በኢትዮጵያ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ውስጥ የሚታየውን ኋላቀር የሥራ አመራር ዘዴን በአዳዲስ እና ዘመናዊ የሥራ አመራር ዘይቤዎች በመቀየር የሚገኝ የእውቀት ሽግግርን እውን ለማድረግ፣ ተቋማቱን በመሸጥ ከሚሰበሰብ ገቢ በአሁኑ ወቅት የግሉ ዘርፍ ሊሳተፍባቸው ያልቻላቸውን ዘርፎች በመክፈት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት እና እነዚህ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ያለባቸውን የፋይናንስ ይዞታ በማጠናከር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነታቸው ተጠብቆ የሚዘልቅበትን አቅም ከመገንባት አኳያ ፕራይቬታይዜሽን አስፈላጊ እንደሚሆን ታምኗል።

እነዚህ በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ የማዞር ሂደት በምን መልኩ መፈፀም ይገባል? የሚለውን ጥያቄ ከዚህ ቀደም የተካሄዱ አንዳንድ እርምጃዎችን ለአብነት በማንሳት ጉዳዩን ለማስረዳት ልሞክር። የኢትዮጵያ መንግሥታት የገነቧቸው (የወረሷቸው) ሦስት ትላልቅ የቢራ ፋብሪካዎችን ለሽያጭ በማቅረብ አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማግኘት የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኮፖርሬሽን የመሳሰሉ ተቋማትን መመሥረት መቻሏን ሲነገር ይደመጣል፡፡ በመሠረቱ ይህ እርምጃ ትክክለኛም ተገቢም ይመስላል። እነዚህ የቢራ ፋብሪካዎችን በመንግሥት ይዞታ ሥር ማቆየቱ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለውምና።

በተመሳሳይ ወቅቶች በአገሪቱ ውስጥ አዳዲስ የቢራ ፋብሪካዎች (ዳሽን፣ ራያ፣ ሃበሻ እና በቅርቡ ደግሞ ዘቢዳር የሚባሉ ዜጐች በመሠረቷቸው አክስዮን ማህበራት አማካኝነት ተቋቁመው) መገንባታቸውን ሰምተናል፡፡ በመሆኑም በመንግስት ይዞታ ስር የነበሩትንና ለውጭ አገር ኩባንያዎች የተዛወሩትን የቢራ ፋብሪካዎች በአገሪቱ ዜጐች ሥር እንዲገቡ ማድረግ አይቻልም ነበር ወይ? ከወጭ የመጡት እነ ሄኒከን ወደ አዳዲስ ፋብሪካ ምሥረታ እንዲያተኩሩ ማድረግስ አይቻልም ነበር ወይ?

እነዚህን ጥያቄዎች ለማንሳት ያስደገደኝ ከአደጉት አገሮች እነ እንግሊዝ በ1980ዎቹ በታቸር የሥልጣን ዘመን የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ ያዞሩበት አብነት እጅግ አስደናቂ ሆኖ ስላገኘሁት ነው። ማርጋሪት ታቸር የእንግሊዝ ኢኮኖሚ ከገባበት አዙሪት እንዲወጣ ከወሰደቻቸው እርምጃዎች መካከል የፕራይቬታይዜሽን እርምጃ አንዱ ነበር። በዚህም ብሪቲሽ የባበቡር አገልግሎት፤ ብሪቲሽ ቴሌኮሚዩኒኬሽን እና ብሪቲሽ ጋዝ ካምፓኒዎች ከመንግሥት ወደ ግል ይዞታነት እንዲዘዋወሩ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የድርጅቶቹ ሽያጭ እያንዳንዱ እንግሊዛዊ የቦንድ ግዢን እንዲፈጽም በማድረግ የሀብት ባለቤት እንዲሆን የማስቻል እርምጃ ነበር የወሰደችው፡፡ እርምጃው በአንድ ወገን መንግሥት በሥሩ የሚገኙ ተቋማትን ወደ ግል ይዞታ በማዘዋወር ኢኮኖሚው በተሻለ መንገድ እንዲቀሳቀስ ማድረግ ሲያስችል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሀብት ይዞታው ከመንግሥት ወደ ህዝብ እንዲዞር ማድረግ አስችሏል፡፡ በዚህም የአገር ሀብትነቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ የተቻለበት እርምጃ ነበር ማለት ይቻላል።

ከዚህ አብነት የምንማረው መንግሥት ተቋማቱን ይዞ አላስፈጊ ጫና ውስጥ ላለመግባት ሲል ከእጁ ሲያስወጣ የባለቤትነት ይዞታውን ወደ ህዝብ በማዘዋወር ዜጐችን ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለበት ነው። በቅርቡ ከመገናኛ ብዙኃን እንደተደመጠው የኢትዮጰያ መንግስት ያስገነባቸውን አሥር አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች ወደ ግል ይዞታ የማዞር ሃሣብ እንዳለው እየተደመጠ ነው። ይህን ውሳኔ ተገቢ እርምጃ አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡ ምክንያቱም አሁን ያሉንን የስኳር ፋብሪካዎች እንኳን ማስተዳደር አቅቶን የስኳር ፋብሪካዎቻችን ያሉበት ውጥንቅጥ ሁኔታ የሚታወቅ ነውና፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ፋብሪካዎች ይዞታን ለውጭ ዜጐች እንዲሸጥ በማድረግ መገላገል አለብን ብዬ አላምንም፡፡ ቅድሚያ ለኢትጵያን ዜጐች በአክሲዮን መልክ መሸጥ እንችላለን። ይህንን ሀብት ወደ ዜጐች የማዘዋወር ተግባር በተለያዩ መንገዶች ተፈፃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የግል ባንኮች የተወሰነውን ድርሻ እንዲይዙ ማድረግ ይቻላል።

የውጭ ምንዛሪም ማፍራት ካስፈለገ የአክሲዮን ሽያጩን በውጭ አገር ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበትን መንገድ በመቀየስ እነሱም ተጠቅመው አገርን እንዲጠቀሙ ማድረግ ይቻላል። ሲጠቃለል ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚጠጋው ድርሻ በዜጐቻችን እጅ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ቀሪውን ድርሻ ለውጭ ዜጐችና ኩባንያዎች መስጠት ይቻላል። ይህንን ማድረግ ከተቻለ አገራዊ ሀብትነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥትም ፍላጐቱን ማሟላት ይችላል ማለት ነው።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅትንም ሽያጭ አስመልክቶ የቀረቡት ዜናዎች እውነት ከሆኑ ከላይ ባስቀመጥኩት መንገድ መፈፀም ይኖርባቸዋል። እንደተባለው የመርከብ ድርጅቱ 40 በመቶ ድርሻ ለቻይናውያን ባለሀብቶችን እንዲዞር የሚደረግ ከሆነ ጉዳዩ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ምክንያቱም የመርከብ ድርጅቱን እንደ ስኳር ፋብሪካዎች አቅልለን የምንመለከተው ንብረት አይደለም። ይህ ሀብት አገሪቱ ካሏት እስትራጂካዊ ሀብቶች አንዱ ነው በመሆኑም እንዲህ በቀላሉ አውጥተን ለሌሎች ዜጐች የምንተወው መሆን አይኖርበትም።

ወሳኝ የሆነውን ድርሻ እስከያዝን ድረስ የተወሰነውን ለውጭ ዜጐች ብንተወው ችግር የለም በሚል የሚከራከሩን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ነገሩ እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይህ ሀብት ካለው ፋይዳ አንፃር ገዢ ሆነው የቀረቡት ቻይናውያን ፍላጐታቸውን በግልፅ የማናውቀው መሆኑ ነው። አንድ ከዚህ ቀደም በአገራችን የተከሰተ አብነት አንስቼ ለማሳየት ልሞክር፡፡ እ..አ በ1990ዎቹ መጀመሪያ በመከላከያ ሥር የሚተዳደር ላሊበላ በመባል የሚታወቅ ጠንካራ የኮንስትራክሽን ድርጅት መፍጠር ተችሎ ነበር። ድርጅቱ የመንግሥት ልማት ድርጅት ቢሆንም የሥራ አፈጻጸሙን እንቅስቃሴው በግል ከተቋቋሙ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች እጅግ የላቀ ደረጃ ላይ በመድረስ የአገራችን ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪን ተስፋ የፈነጠቀ ነበር፡፡

ይህን አካሄድ የተረዱት የቻይና ኮንስትራክሽን ካምፓኒዎች የድርጅቱን እድገት እንደሥጋት በመቁጠራቸው የጋራ ሽርክና (Joint venture) እንመሥርት ብለው በመቅረብ ካግባቡና ከመሠረቱም በኋላ ድርጅቱ ተመልሶ ኢንዱስትሪው ውስጥ እንዳይሰራ በሚያደርግ መልኩ አሽመድምደው እና አድቅቀው ከገበያ እንዲወጣ አድርገዋል፡፡ በዚህም በዘርፉ የተስፋ ጭላንጭል ይዞ የተነሳውን ድርጅት አጠፉ፡፡

ስለሆነም ካፒታሊዝም በምዕራቡ ዓለምም ሆነ በቻይና የመላዕክት ምስል ተላብሶ ቢቀርብ ሰይጣንነቱ ለጊዜው ይደበቅ ይሆን እንጂ ፈፅሞ እንደማይጠፋ መታወቅ ይኖርበታል። በመሆኑም ከኢትዮጵያ መርከቦች ድርጅት ጋር ሊፈጠር የታሰበውን የሽርክና እንቅስቃሴም ከእነዚህ መሰል እኩይ ተግባራት አንፃር መፈተሽ ይኖርበታል። የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት በአፍሪካ ቀንድ ወይም በምሥራቅ አፍሪካ ጐልቶ እየወጣ ያለ ግዙፍ እና እስትራተጂካዊ ቀጠሜታ ያለው ተቋም መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

ይህ ተቋም እንደማናቸውም የኢትዮጵያ ድርጅቶች የሥራ አመራር (የማኔጅመንት) ድክመት የለበትም የሚል ቅዠት የለኝም፡፡ ውስጡ ቢፈተሽ በርካታ ጉድለቶች እንደሚኖርበት ያለጥርጥር መናገር ይቻላል። ስለሆነም ትክክለኛውን የበሽታ ክፍል ፈልገን ተገቢውን ህክምና እና ፈውስ መስጠት እንጂ የበሽታውን ምልክቶች (symptom) በማየት መድኃኒት ፍለጋ መሄዱ ውጤት እንደማያመጣ እሙን ነው። የዚህ ድርጅት መፍትሔ (Management contract) በመስጠት ሊፈታ የሚችል ነው፡፡ በመሆኑም ተቋሙን ወደ ግል ይዞታ የማዞር ተግባር ውስጥ ከመግባታችን በፊት ውይይቶች ይካሄዱ፤ የሃሣብ ልዩነቶች በስፋት ይንሸራሸሩ፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ወደ ትክክለኛው የመትሔ አቅጣጫ እንደርሳለን።

 

ሮባ ቶኪቻው

Published in ኢኮኖሚ

   

ማርክስ ጋርቬ                                           ዶክተር ኩዋሚ ኑክሩማ                                 ማርቲን ሉተርኪንግ

 

እኤእ የካቲት 1ቀን 1965 ለጥቁር አሜሪካውያን ልዩ ቀን ናት። በዚች ዕለት ጥቁሮች በአሜሪካ የመምረጥ መብት እንዳይኖራቸው የሚደነግገውን ህግ ለማውጣት የህግ አውጭው አካላት በአሜሪካ ዳላስ ከተማ ተሰብስበዋል። ይህንኑ ህግ በመቃወም ማርቲን ሉተርኪንግ 3 መቶ የሚሆኑ ጥቁር አሜሪካውያኖችን አሰልፈው አደባባይ ወጥተዋል። ይህ ድርጊታቸው ነው ማርቲን ሉተርኪግን ለእስር የዳርጋቸው። ይች ዕለትም በነፃነት ታጋዮች ታስባ ትውላለች፡፡

የጥቁሮች የነፃነት ትግል እ..አ በ1916 በማርክስ ጋርቬን እንደተጀመረ ታሪክ አስፍሯል፡፡ የጥቁር የነፃነት ታጋዮች አፍሪካ ከአውሮፓዎች ቅኝ ዥዎች ነፃ በመሆን ጥቁሮች በአንድነት የሚኖሩባት አህጉር መሆን አለባት ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ይህን እቅዳቸውን ለማሳካት ዓለም አቀፍ የጥቁሮች ማህበር «ዩኒቨርሳል ኔግሮ ኢንፕሩቭመንት አሶሴሽን» በማቋቋም እንቅስቃሴ ጀመሩ። ማህበሩ በሶስት አመት ውስጥ ከካሪቢያን ፣ ከላቲን አሜሪካ እና ከአፍሪካ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አባላትን ማፍራት ችሏል፡፡ ሁሉንም ጥቁሮች ወደናት ምድራቸው አፍሪካ ለማጓጓዝ የሚያስችል የጥቁር ኮከብ አንበሳ የሚባል የመርከብ ኩባንያ አቋቁመው ነበር፡፡ ጋርቬን በመረጃ ማጭበርበር ወንጀል ከአሜሪካ እንዲወጣ ከተደገ በኋላ የጥቁሮችን የነፃነት እንቅስቃሴ ማህበር ጠንካራ መሪ ባለማግኘቱና በገንዘብ እጥረት ዩኒቨርሳል ሊፈርስ ችሏል፡፡

ፓን አፍሪካኒዝም በነጮች ቅኝ ግዛት ስር የነበሩትን አፍሪካውያንን ነፃ ለማውጣት ጥቁር አሜሪካዊያን የጀመሩት ትግል ነው፡፡ በየመጀመሪው ፓን አፍሪካኒዝም ጉባኤ በታላቋ ብርታኒያ ለንደን ከተማ እ..1900 በሄነሪ ሳይሊቪስተር ዊሊያም ሰብሳቢነት ተካሂዷል፡፡ እ..1900 እስከ 1994 ሰባት የፓን አፍሪካን ጉባኤዎች በ1919 ፓሪስ፣ 1921 ለንደን፣ 1923 ብራሰልስ፣ 1927 ኒዎርክ፣ 1945 ማንችስተር ላይ የተካሄዱ ሲሆን ሁሉንም ጉባኤዎች የአፍሪካ አሜሪካውያን የመሩት እንቅስቃሴ እንደሆነ ይታወሳል፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1958 ለመጀመሪያ ጊዜ ጉባኤው ነፃ በወጣችው የጋና ዋና ከተማ አክራ ላይ ተካሂዷል፡፡

በወቅቱ የጋና ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶክተር ኩዋሚ ኑክሩማን የአፍሪካ ሀገሮች መከፋፈል ያዳክማቸዋል የሚል እምነት ስለነበራቸው እ..1962 በፃፉት መጽሃፋቸው አፍሪካ አንድ ሀገር መሆን አለባት ብለዋል። ይህ የአፍሪካ ሀገሮች ፖለቲካዊ አንድነት መመስረት አለባቸው ብለው የሚያራምዱት አቋማቸውም በብዙ ሀገሮች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። ይልቁንስ የኢኮኖሚ ውህደት ይቀድማል ብለው በሚያስቡ መሪዎች ሚዛኑ በማጋደሉ እ..አ ግንቦት 25 ቀን 1963 ከቀኝ ግዛት ነፃ የወጡ 32 የአፍሪካ ሀገሮች በመዲናችን አዲስ አበባ የቀድሞውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የአሁኑን የአፍሪካ ህብረት ለመመስረት ከስምምነት ደርሰዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ዋነኛው አላማ አንድነትን መደገፍ፣ አፍሪካውያን የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ እርስ በራሳቸው የሚኖራቸውን ትስስር መደገፍ፣ የአህጉሪቷን ሉአላዊነት ማስጠበቅ እና በአባል ሀገራት መካከል ጥሩ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲኖር ማስቻል የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ሆኖም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና ወታደራዊ አቅምና ሀይል ስላልነበረው በአህጉሪቷ ውስጥ ይከሰቱ የነበሩ የእርስ በእርስ ግጭቶችን ለመከላከል፣ መፍታትና መቀነስ አልቻለም፡፡

ድክመቶችን መቅረፍ እንዲቻል ሀምሌ እ..9 ቀን 2002 የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የአፍሪካ ህብረት ተክቶታል፡፡ ህብረቱም ዋነኛ አላማው በአባል ሀገሮች መካከል ትስስር መፍጠር፣ ብልፅግናን በአህጉሪቷ ማስፈን፣ ለሰላም መስራት እና የአባል ሀገራትን ሉአላዊነት መጠበቅ ነው፡፡ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሚለየውም በአባል ሀገራት የጦር ወንጀል፣ የዘር ማጥፋት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲኖር ጣልቃ የመግባት ስልጣን እንዲኖረው ተካቷል፡፡ ሆኖም ሊቢያ በነበረው ብጥብጥ፣ ርዋንዳ በተካሄደው የዘር ማጥፋት እንዲሁም ሱዳን ዳርፉር የነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ቶሎ በመግባት ችግሩን መፍታት አልቻለም፡፡ ድክመቶች ቢኖሩም በብሩንዲ፣ ቶጎ ፣ ሱዳን እና ሶማሌ ወታደሮቹን በመላክ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት መስራቱ ይታወቃል፡፡

አዲስ አበባ እኤእ ጥር 20/2009 አገሮች የፓን አፍሪካ ፓርላማ የሕግ አውጪነት ሚና እንዲኖረው የተዘጋጀውን ፕሮቶኮል ባለማጽደቃቸው ፓርላማው የተቋቋመበትን ዓላማ መወጣት ያለመቻሉን ገልጸዋል። ፓርላማው አሁን ካለበት የአማካሪነት ሚና ወደ ሕግ አውጪነት እንዲሸጋገር የፕሮቶኮሉ መጽደቅ አስፈላጊነት "የጎላ ነው" ተብሏል።

ሰሞኑን በመዲናችን አዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት 28ኛው የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን የኅብረቱ አንድ አካል የሆነው የፓን አፍሪካ ፓርላ መግለጫ ሰጥቷል። የፓርላማው ፕሬዚዳንት ሚስተር ሮጀር ንኮዶ ዳንግ እንደገለጹት፤ ከሶስት ዓመታት በፊት በአህጉሪቷ መሪዎች የጸደቀው ፕሮቶኮል እስካሁን በአገር ደረጃ ሊጸድቅ አልቻለም። ‹‹ፕሮቶኮሉ በአህጉር ደረጃ እንዲጸድቅ ሃያ ስምንት አባል አገሮች መፈረም ይኖርባቸዋል›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ እስካሁን ፕሮቶኮሉን ለማጽደቅ 14 አገሮች ብቻ ፈርመዋል ብለዋል።

..አ በ2014 በኢኳቶሪያል ጊኒ ማላቦ ከተማ በተካሄደው 23ኛው የኅብረቱ ጉባኤ ላይ የፓን አፍሪካ ፓርላማ የሕግ አውጪነት ሚና እንዲኖረው የሚደነግገው ፕሮቶኮል መጽደቁ ይታወሳል። እስካሁን ከ54 የኅብረቱ አባል አገሮች መካከል ሴራሊዮን፣ ማሊ፣ ጋምቢያ፣ ሳሃራዊ አረብ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክና ቶጎ ብቻ ናቸው ፕሮቶኮሉን ያጸደቁት። "ፓርላማው የሕግ አውጪነት ሚናውን ካላገኘ በስተቀር አፍሪካ በአንድ ድምጽ መናገር አትችልም" ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

አዲሱ የአፍሪካ ኅብረት በጀት አሰባሰብ መመሪያ ከተያዘው የፈረንጆች 2017 ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ኅብረቱ አስታውቋል። የአፍሪካ ኅብረት ምክትል ኮሚሽነር ኢራስተስ ምዌንቻ የኅብረቱን አጀንዳዎችና ተልዕኮዎች ማስፈጸሚያ ገንዘብ አሰባሰብን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር።

በዚህም በተጠናቀቀው እኤእ 2016 ዓመት የኅብረቱ ዓመታዊ በጀት 447 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 75 በመቶ ያህሉ ከደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ አልጄሪያ፣ ሊቢያና ግብጽ በተገኘ ገንዘብ ተሸፍኗል። የኅብረቱን ተልዕኮዎች ለማስፈጸም የሚያስፈልግ በጀትን ሁሉም አባል አገራት መሸፈን የሚጠበቅባቸው ቢሆንም ውስን አገራት ወጪውን መሸፈናቸው በኅብረቱ አሰራር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲሱ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር የኅብረቱ አባል አገራት ወደ አገራቸው ከሚገቡ ምርቶች የገቢ ቀረጥ ውስጥ 0 ነጥብ 2 በመቶ ያህሉን እንዲሰጡ የሚያስገድድ ሲሆን የኅብረቱ መሪዎች መርሃ ግብሩን እንደሚያጸድቁት ይጠበቃል። ኅብረቱ ለሚያከና ውናቸው የተለያዩ ሥራዎች የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከውስን አገራት ወይም ከበለፀጉ አገራት ማግኘቱ በአጀንዳ 2063 የበለፀገችና የተረጋጋች አህጉር ለመፍጠር በያዘው ዕቅድ አፈፃጸም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል ብለዋል።

በዚህ ዓመት በሚተገበረው አዲሱ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር መሰረት በየዓመቱ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከአባል አገራቱ እንደሚገኝ አመልክተዋል። በዚህ መሰረት በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ለኅብረቱ ሥራ ማስኬጃ የሚውለውን በጀት ሙሉ በሙሉ በአባል አገራት የሚሸፈን ይሆናል። በተመሳሳይ ለልማት ሥራዎች ከሚያስፈልገው አጠቃላይ በጀት ውስጥ 75 በመቶና ለሰላምና ፀጥታ ስራዎች ከሚያስፈልገው በጀት 25 በመቶ ያህሉን በራስ አቅም ለመሸፈን ታስቧል። ይህ አህጉሪቱ የእድገት ጉዞ ያሳያል፡፡ እናም የአፍሪካዊያን በነፃነት ትግሉ የነበራቸውን ግለት ጠብቀው በኢኮኖሚውና በፖለቲካው መስክ ለመድገም ከፊታቸው ብዙ ስራ ይጠብቃቸዋል ።

 

አየናቸው እሸቱ

 

 

 

Published in ዓለም አቀፍ
Wednesday, 01 February 2017 17:29

እኛና የዘነጋነው ሳጥናችን

 

ኢትዮጵያ ውስጥ ሦስት ሳጥኖች አሉን፡፡ ሁለቱ ሳጥኖች በጣም ይፈልጋሉ፡፡ ስለሚፈልጉም አይኖች ሁሉ ከእነሱ አይነቀሉም። አንደኛውን ሳጥን ግን ዞሮ የሚያየው የለም፡፡ ሁለቱ በውስጣቸው በጣም ተፈላጊ ነገር አለ ተብሎ ስለሚታመን ሳጥኖቹ በፖሊስ በዘበኛ፣ አንዳንዴም በወታደር ይጠበቃሉ ፤ አንደኛው ሳጥን ግን ጠባቂ የለውም፡፡ ውስጣቸው ያለው ነገር ሲጨምር የሚያመጡት ለውጥ አለ ተብሎ ስለሚታሰብ ሁለቱ ሳጥኖች ቶሎ ቶሎ ይቆጠራሉ፡፡ አንደኛው ሳጥን ግን የሚያስታውሰው የለም፡፡_

ሁለቱ ሳጥኖች የምርጫ ሳጥንና የገንዘብ ሳጥን ናቸው ፡፡ አንዱ ውስጥ ሥልጣን፣ ሌላው ውስጥ ገንዘብ አለ፡፡ ሥልጣን ያለበትን ሳጥን ፖለቲከኞች ይፈልጉታል፡፡ ስለዚህም በአንክሮ ይከታተሉታል፤ ይጠብቁታል፡፡ ገንዘብ ያለበትን ሳጥን ደግሞ ሙሰኞች ይጓጉለታል፡፡ ሲያመቻቸውም ይሰብሩታል፤ ይገለብጡታል፡፡ ሕዝቡም ስለእነዚህ ስለሁለቱ ሳጥኖች ጉዳይ ይከታተላል፡፡ ሲዘጉና ሲከፈቱ ኮሚቴ ያቋቁማል፡፡ ሲቆጠሩና ሲመዘኑ ማወቅ ይፈልጋል፡፡ ሥልጣንና ገንዘብ ስላለባቸው፡፡

ሦስተኛው ሳጥን ግን ከእነዚህ ሁሉ ይለያል፡፡ ዘጊ እንጂ ከፋች የለውም፡፡ ሠሪ እንጂ ተከታታይ የለውም፡፡ በውስጡ ያለውን ነገር ለማወቅ ባለቤቱም፤ ሕዝቡም አይጓጉም፡፡ ማንም እንደልቡ ያገኘዋል፡፡ ግን አይጠቀምበትም፡፡ ጥበቃ የለውም፤ ግን ማንም አይሰብረውም፡፡ ተመልካች ያጡ ወረቀቶችን በውስጡ እንደያዘ በየግድግዳው ላይ አርጅቷል፡፡ ሰዉም በዚህኛው ሳጥን ውስጥ ለማስገባት ብዙም አይፈልግም፡፡ እንደ ሁለቱ ሳጥኖች_ ፈላጊ የለውም ብሎ ያምናልና፡፡_

ለምን?

ምክንያቱም ሦስተኛው ሳጥን ‹የሐሳብ መስጫ ሳጥን› ስለሆነ፡፡ ዓለምን የቀየረው ሐሳብ ቢሆንም እኛ ሀገር ግን ብዙም ፈላጊም ተጠቃሚም ያለው አይመስልም ፡፡ መሥሪያ ቤቶችም የተሰጣቸውን እርዳታ እንጂ የተሰጣቸውን ሐሳብ ሪፖርት አያደርጉም፡፡ ዋናው ኦዲተርም የመንግስት ተቋማት የተሰጣቸውን ገንዘብ የት እንዳደረጉት እንጂ የተሰጣቸውን ሐሳብ የት እንዳደረሱት አይጠይቃቸውም፡፡ ሀገር የምታድገው፣ የምትለወጠውና የምትሠለጥነው ግን በሐሳብ ነው፡፡ ያውም በሰላ ሐሳብ፡፡ ያደጉ ሀገሮች ማለት ታላላቅ አሳቢዎችና ታላላቅ ሐሳቦች ያሏቸው ሀገሮች ማለት ናቸው ይለናል ዳንኤል ክብረት የዳንኤል እይታዎች በተባለ የጡመራ ገጹ ላይ፡፡ (የተወሰነ ማስተካከያዎችን አድርጌበታለሁ)

ዳንኤል እንዳለው አገራችን ሀሳብ የሚደመጥባት የሀሳብ መስጫ ሳጥኖች የሚበረበሩባት ብትሆን ብዙ ለውጥ ማምጣት፤ ብዙም ታምር መስራትና ገብተንበት ወደነበረው የቀውስ አዙሪት ውስጥም ባልገባን ነበር፡፡ ምክንያቱም የሀሳብ መስጫ ሳጥኑ ውስጥ ሞልተው የተረፉም ብቻ ሳይሆን የፈሰሱም ጭምር የህዝብ ብሶቶችና ጥያቄዎች ነበሩና ነው፡፡

የሀሳብ መስጫ ሳጥኖቻችን የብሶት፣ የበደል፣ የፍትህ ማጣት ጩኸት የታመቀባቸው ናቸው። እነዚህ ሳጥኖች የሌሉበት ተቋም በአገራችን ይኖር ይሆን? በጭራሸ። ነገር ግን እነዚህ ሀሳቦች ፈላጊ ስለሌላቸው፤ አለ ከተባለም ምን አሉ ምን ተባለ ብሎ የሚከታተላቸው ስለሌለ ሳጥኑ ውስጥ እንዳሉ አሉ። ይህ የተቋማት ድምር ውጤትም ሄዶ ሄዶ በመደማመጥ እጦት አገር ላይ ያመጣውን ችግር ሁላችንም ያየነው ነው። ሰው በባህሪው ከሰው ጋር ለመጋጨት ባለመፈለግም ይሁን በሌላ ምክንያት በአንድ ተቋም ላይ ወይንም በአመራሩ ላይ አለ ብሎ የሚያምነውን ችግር በሀሳብ መስጫ ሳጥኖች ውስጥ ያስቀምጣል። ነገር ግን እነዚያ ሀሳቦች አስታዋሽ የላቸውም። ቢኖራቸውም ውግንናው ለአሰራሩና ተጥሷል ለተባለው መመሪያና ደንብ አሊያም ለመፍትሄው ሳይሆን ለተቋም ኃላፊ ይሆንና ሃሳቡ ሀሳብ ብቻ ሆኖ ሳጥኑ ውስጥ ተቀብሮ ይቀራል።

ጥር 1 ቀን 2009 .ም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች መግለጫ መስጠታቸው አይዘነጋም። በዚሁ መግለጫቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በርካታ ቁምነገሮችን ተናግረዋል። አድምጠናልም። ኢሕአዴግ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሎ በኢትዮጵያ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የፍትሐዊ አስተዳደር ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ የሠራ ድርጅት ነው፡፡ (ምንም ጥርጥር የለውም፤ እውነት ነው) በየጊዜው ራሱን በራሱ እያረመ የዘለቀም ድርጅት ነው፡፡ የሚመራው መንግሥትም እንደዚሁ ራስን በራስ የማረም መርህ ተከትሎ የመጣ መንግሥት ነው፡፡ ስለዚህ በቅርቡ ያካሄደው ተሃድሶም በዚህ መርህ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ (ይሄም የሚካድ ሀቅ አይደለም)

አቶ ኃይለማርያም እንደተናገሩትም፤ ሥርዓቱን የሚያጋጥሙ አደጋዎች ተለይተዋል። በተለይም በአመራር ላይ ያለው አካል ቀስ በቀስ የራሱን ኑሮ ለማሻሻል የግል ብልፅግናውን የመፈለግ፣ ከዚያም አልፎ የቆመለትን ዓላማ እየሸረሸረ የመሄድ ችግሩ ሥርዓቱን ለሀሜትም ብቻ ሳይሆን አደጋ ውስጥ ጥሎታል። እርሳቸውም አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ይሄንኑ ነው፤ "የመንግሥትን ሥልጣን የምናይበትን መንገድ በምንፈትሽበት ጊዜ በሌብነትና በሙስና የሚገለጽ የመጨረሻው ደረጃ ብልሹነት አለ፡፡ ከዚህም ባሻገር የያዘውን ሥልጣን ለሕዝብ አገልግሎት መጠቀም ሲገባ ኑሮውን፣ ቤተሰቡን፣ ሕይወቱን በመምራት ዙሪያና ምቹ ኑሮ ለመኖር የመሞከር ነገር ተስተውሏል፡፡ ባይሰርቅ እንኳ ስርቆት ድረስ የመሄድ አመለካከት ተለይቷል፡፡ ከዚህ በመነሳት እጅግ አብዛኛውን አመራር እያጠቃ ያለው ለሥራ ከመትጋትና መስዋዕትነት ከመክፈል ይልቅ መዝናናትን የመምረጥ፣ ባለጉዳይን ያለማስተናገድ፣ ቢሮ ያለመገኘት ወይም ዝግ መሆን፣ ከሥራ ሰዓት ውጪ ያለመሥራት፣ እንደ ማንኛውም ሲቪል ሠራተኛ 1130 ሰዓት ሲሆን ከቢሮ ወጥቶ መሄድ፣ የተለያዩ ጉዞዎችን የማብዛትና የመሳሰሉት ውጤታማ የማያደርጉ ዝንባሌዎች ይታያሉ፡፡"

እኔም የምለው ይሄንን ነው። እንድ ሁለቱ ሳጥኖች ሁሉ የማይገለበጡት ወይንም የማይከፈቱት የሀሳብ መስጫ ሳጥኖች እነዚህን ችግሮች አስቀድመው አላመለከቱም? አልጠቆሙም ነበር ወይ? በዚህ ደረጃ የማቀርበው ማስረጃ ባይኖረኝም ይህ አምድ ነጻ አስተያየት የሚስተናገድበት ነውና ሃሳቤን መግለጽ እወዳለሁ። ከፍተኛው አመራር የሚመራው ተራውን ሰራተኛ ነው። ተራው ሰራተኛ ደግሞ ትልቁን መሪውን ደፍሮ የሚሄስበት ባህሉና ልምዱ ስለሌለው ሃሳቡን የሚያቀርበው በእነዚያ ሳጥኖች ውስጥ ነው። ሳጥኖቹ ግን የሚያያቸው ስለሌለ፤ ወይንም የሚያያቸው ራሱ ስለሆነ መፍትሄ ከማፈላለግ ይልቅ እዚያው ደፍቆ የማስቀረት ዝንባሌ የለም ብሎ መከራከር አይቻልም።

ምክንያቱም አሁን በተሀድሶው ነጥረው የወጡና የከፍተኛ አመራሩ ችግሮች አስቀድሞ ህዝብ የሚያውቃቸው፤ በአንድም በሌላ መንገድ ሲናገራቸውና ሲገልጻቸው የኖሩ ናቸው። ነገር ግን እነዚህን የሀሳብ ሳጥኖች (ሳጥን ስል የግድ በቁልፍ የተከረቸመ ቁሳዊውን ሳጥን ማለት ብቻ እንዳልሆነ አንባቢ ይረዳልኝ) ልብ ብሎ የተመለከታቸው ስላልነበረ የገባንበት ችግር ውስጥ ሁሉ ልንገባ ችለናል። በተለይም በሙስና ዙሪያ።

ወደ ተሀድሶ ከተገባ በኋላ መንግስት በተለያዩ ችግሮች ትራስነት አንድ አመት ብቻ ያስቆጠረውን ካቢኔ አፍርሶ በአዲስ መልክ እስከማቋቋም የዘለቀ የአመራር ለውጥና ሽግሽግ አድርጓል። እዚህ ላይ አቶ ኃይለማርያም በመግለጫቸው የተናገሩትን እንዳለ ላቅርብ፤ "በሙስና ተሳትፎ ማስረጃ የተገኘበት በምንም መልኩ ተጠያቂ ሳይሆን ሊቀር አይችልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጥርጣሬዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ወደ ሕግ ተጠያቂነት ለመውሰድ በቂ ማስረጃ ሊኖር ይገባል፡፡ ጥርጣሬዎች በሚኖሩበት ጊዜ ሊወሰዱ የሚችሉ ዕርምጃዎች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው አስተዳደራዊ በሆነ መንገድ ከሥልጣኑ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ ከሥልጣኑ ከወጣ በኋላ በቂ ማስረጃ ካለ ወደ ሕግ ቀርቦ ይጠየቃል፡፡ በቂ ማስረጃ ሳይኖር ወደ ሕግ አቅርቦ ማሸነፍ ስለማይቻል ትርጉም የለውም ማለት ነው፡፡ ሙስና በጣም ውስብስብ የሆነ ወንጀል ነው፡፡ የተቻለውን ያህል ባገኘነው በቂ ማስረጃ አመራሮችን ተጠያቂ እያደረግን መጥተናል፡፡ ነገር ግን በዚህ ያበቃል ማለት አይደለም፡፡

"ሙስና ውስብስብነቱ ታውቆ አሁን ከሥልጣን የወረዱ፣ እንዲሁም በሥልጣን ላይ ያሉና በሙስና የተሳተፉትን በየጊዜው በጥናት ላይ በመመሥረት የማፅዳት ሥራ መከናወን አለበት፡፡ ሁለተኛው በተሃድሶ ንቅናቄው ውስጥ እንደ ሥርዓት ሊቀመጥ ይገባል ብለን ያቀድነው ኅብረተሰቡ በፀረ ሙስና ትግል ውስጥ በስፋትና በጥልቀት የሚሳተፍበትን ሁኔታ ማመቻቸት ማስረጃዎችን ለማግኘት ወሳኝ መሆኑን ነው፡፡ … ኅብረተሰቡ ማስረጃ በማቅረብ የሚሳተፍበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለብን፡፡ ከዚህ አኳያ መንግሥት የወሰነው የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አቋቁሞ ኅብረተሰቡ ለዚህ ማዕከል በየጊዜው ማስረጃዎችንና መረጃዎችን የሚሰጥበት ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡"

የእኔም ነጥብ ያለው እዚህ ላይ ነው። ይሄ እድል መጀመሪያስ አልተሰጠም ነበር ወይ? በጭራሽ። ህዝቡ የተከለከለው መብት እንዳይጠቁም፤ መረጃም እንዳይሰጥ የተገደበበት እድል አለ ብዬ አላምንም። ነገር ግን ቀደም ብዬ እንዳልኩት በፍርሀትም ይሁን በሌላ ምክንያት ፊት ለፊት መናገርና መጠቆም ስለማይወድና ስለማይደፍርም ጭምር የሀሳብ መስጫ ሳጥን እና መዝገብ የሚል አሰራርም ዘርግቷል። ህዝቡም በእነዚህ መንገዶች ያለውንና የተሰማውን ሁሉ ተናግሯል። ነገር ግን ይሄንን ሀሳብ ወስዶ በልኩ መዝኖና አጣርቶ እርምጃ መውሰድ ላይ መንግስት እጥረት ነበረበት። ስለሆነም ይሄ ችግር ከዚህ በኋላ እንዳይደገም የሀሳብ መስጫ ሳጥኖችም እንደ ሁለቱ ሳጥኖች ሁሉ አይኖች ይረፉባቸው፤ ይጠበቁ፤ ይፈተሹ።

ካነሳሁት ሀሳብ አንጻር መንግስት በአዲስ መንገድ ለመጓዝ ቃል ገብቷል፤ ቃሉንም በተግባር መግለጥ ጀምሯል። ምክንያቱም፤ አቶ ኃይለማርያም፤ "የመንግሥት ባለሥልጣናት ሀብትና ንብረት ይፋ የሚሆንበትን ሁኔታ በማመቻቸት፣ ይፋ ከሆነው በተጨማሪ ‘እከሌ የተባለ ባለሥልጣን ንብረት አለው’፣ ‘በራሱ ብቻ ሳይሆን በዘመዶቹ ወይም በወዳጆቹ የተያዘ ሀብት አለው’ በማለት እንዲጠቁሙ ለማድረግ ታቅዷል" ሲሉ ተናግረዋልና።

ከዚህም በተጨማሪ መንግስት የዴሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር ቃል ገብቷል። በተግባርም እያታዩ ያሉ ፍንጮች አሉ። ለአብነት ያህልም ፍትህ ሚኒስቴር ፈርሶ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሆኖ ተቋቁሟል፤ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ስርም እንደ አሜሪካው ኤፍ.. አይ ዓይነት የምርመራ ስራን የሚያከናውን ቢሮ ተቋቁሟል። ይሄ የተዘነጋውን ሳጥን የመፈለግ ስራ ይመስለኛል። ስለሆነም መንግስት በዚህ በኩል አበጀህ ሊባል ይገባል። ህዝቡም ውስጡ የሚብከ ነከንባቸውንና ይሄ የእነ እከሌ ህንጻ ነው፤ እከሌ የተባለው ባለስልጣን ይሄ ይሄ ሀብት አለው እያለ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚናገራቸውን ከቻለ ደፍሮ ወደ አደባባይ ማውጣት፤ ካልሆነም መንግስት በዘረጋቸው አሰራሮች መጠቆም ይኖርበታል።

የህዝብ ሀብት ለህዝብ ጥቅም ብቻ ነው መዋል ያለበት። ሁሉም እየተነሳ በተሰጠው የህዝብ ወንበር ላይ ሆኖ የህዝብን ሀብት መዝረፍ አይገባውም። ወይንም ሲዘረፍና ለዝሪፊያ ሲጋለጥ እያየ መመልከት ነውር ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ ዓመታዊ በጀት ከዓመት ወደ ዓመት እያደገ ነው፡፡ ለአብነት ያህል እንኳን ብንመለከት በ1984 .ም አራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር የነበረው አጠቃላይ የአገሪቷ በጀት ዘንድሮው በከፍተኛ ሁኔታ አድጎ 274 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ እንዲያውም ሰሞኑን ተጨማሪ 18 ቢሊዮን ብር አጽድቋል።

ይሄ በጀት ለተቀመጠለት ዓላማ በትክክል ከማዋል አንጻር ግን ችግሮች እየታዩ ስለመሆናቸው የዋናው ኦዲተር መስሪያ ቤት የሚያወጣቸው የሂሳብ ምርመራ ውጤቶችን ብቻ መመልከት በቂ ነው። መስሪያ ቤቱ ከ2005 .ም ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት በመንግስት አስፈጻሚ ተቋማት ላይ ባደረገው ኦዲት 23 ቢሊዮን ብር የፋይናስ ህጎች ከሚፈቅዱት ውጪ ስራ ላይ መዋሉን በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።

23 ቢሊዮን ብር። ይሄ ሁሉ ሲሆን ህዝብ አያውቅ ይሆን? የሀሳብ መስጫ ሳጥኖቻችን ይሄንን አስቀድመው አልተናገሩ ይሆን? አመራሩስ ይሄንን ችግር አልተረዳውም ነበር ማለት ይቻላል? በግሌ አይመስ ለኝም። ያለፈው አልፏል፤ ማሰብና መጨነቅ ካለብን ስለወደፊቱ ነውና የረሳናቸውን የሀሳብ መስጫ ሳጥኖችን ዋነኛ የጸረ ሙስና ትግሉ አጋር አድርገን እንቁጠራቸው፤ የዘነጋናቸውን ያህልም ቀልባችንን ሁሉ እንደ ሁለቱ ሁሉ በእነዚህም ሳጥኖች ላይ እናድርግ። አበቃሁ!

 

አርአያ ጌታቸው

 

Published in አጀንዳ

 

ቅኝ ግዛት ያደረሰውን ጫና ከአፍሪካውያን በላይ ጠንቅቆ የሚያውቅ የለም። የቅኝ ግዛትም ሆነ ሌሎች ወራሪዎችን ጥቃት መቋቋም የሚቻለው አንድ ላይ በማበር መሆኑንም አፍሪካውያኑ በድህረ ቅኝ ግዛት ዘመናቸው ተረድተውታል። በዚህም ከአንድነት በላይ የሚያዋጣ ነገር እንደሌለ ተረድተው እ..አ ግንቦት 25 ቀን 1963 ከቀኝ ግዛት ነፃ በወጡ 32 ሀገሮች አማካኝነት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን እዚሁ አዲስ አበባ ላይ መስርተዋል።

ይህ የአፍሪካውያኑ የመጀመሪያው የጋራ መድረክ በሚፈለገው መጠን ጠንካራ ሊሆን ባለመቻሉና፤ ዘመኑ የሚጠይቀውን ዓይነት ድርጅት ባለመሆኑም ጭምር እ..አ በ2002 ወደ ኀብረትነት አድጓል። የኀብረቱ ዋና ዓላማም የተረጋጋችና የበለጸገች አፍሪካን መፍጠር ሆኖ ቀደም ያለው ድርጅት ያልነበሩት ስልጣኖች ሁሉ ተሰጥተውታል።

ለአብነት ያህልም በአባል ሀገራት የጦር ወንጀል፣ የዘር ማጥፋት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲኖር የተሰጠውን ጣልቃ የመግባት ስልጣን መጥቀስ ይቻላል። ኀብረቱ አሁንም ከእነችግሮቹም ቢሆን ባለው አቅም የአህጉሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራቱ ይበል የሚያሰኙ ናቸው። ወደ ብሩንዲ፣ ቶጎ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ ወታደር አዋጥቶ በመላክ የተፈጠሩ ቀውሶችን ለመቆጣጠር ያደረጋቸው ጥረቶቹ አሁንም ለኀብረቱ መልካም ሥራዎች ጥሩ ማሳያዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

ኀብረቱ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ መፍትሄና በአፍሪካውያን በራሳቸው ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት ግን አሁንም ከምዕራባውያን ተፅዕኖ የተላቀቀ ነው ማለት አይቻልም። ምክንያቱም ትናንት በወታደር ቅኝ የገዟትን አፍሪካ ዛሬ ደግሞ በድህነቷ አማካኝነት በእርዳታና መሰል መግቢያ ቀዳዳዎች በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ውስጥ እንዳስገቧት መካድ አይቻልም። ስለሆነም አፍሪካውያን እንደ ትናንቱ ሁሉ ነጻነታቸውን የሚፈልጉት ከሆነ፤ ይፈልጉታልም፤ ከምንም በፊት ያለባቸውን የገንዘብ ወይንም የኢኮኖሚ ጥገኝነት ቢያንስ እንደ ኀብረት ይቀንሱም ብቻ ሳይሆን ያስቁሙ። የኢኮኖሚ ነጻነት የሌለው ኀብረት በምንም መልኩ የፖለቲካ ነጻነት አይኖረውም፤ ሊኖረውም አይችልም።

አፍሪካውያን መሪዎችም በዓመት ሁለት ጊዜ እየተገናኙ የተለያዩ መሪ ቃሎችን በማንገብ ስለአፍሪካና አፍሪካ መምከራቸው በጎ ነገር ነው። ያለባቸውን የጥገኝነት ጥግ ለማሳጠርም አበረታች ሥራዎችን እያከናወኑ ናቸው። በተጠናቀቀው 2016 የኅብረቱ ዓመታዊ በጀት 447 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 75 በመቶ ያህሉ ከደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ አልጄሪያ፣ ሊቢያና ግብጽ በተገኘ ገንዘብ ተሸፍኗል። ይሄ ጥሩ ጅምር ቢሆንም የ54 አፍሪካውያን አገራት ማህበር በአምስት አገራት መዋጮ መሸፈኑ ግን ተገቢ ሊሆን አይችልም።

የኅብረቱን ተልዕኮዎች ለማስፈጸም የሚያስፈልገው በጀት በሁሉም አባል አገራት መሸፈን አለበት። ይሄንን ለማስቀረት ይመስላል በአዲስ አበባ በተካሄደውና ትናንት በተጠናቀቀው 28 መደበኛ ስብሰባቸው አዲስ የበጀት አሸፋፈን መመሪያ አጽድቀው ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቅ ነበር። አዲሱ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር የኅብረቱ አባል አገራት ወደ አገራቸው ከሚገቡ ምርቶች የገቢ ቀረጥ ውስጥ 0 ነጥብ 2 በመቶ ያህሉን እንዲሰጡ የሚያስገድድ ነው። በዚህ ቀመር መሰረትም በየዓመቱ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከአባል አገራቱ ይገኛል የሚል እሳቤ ነበር።

ይህ ገንዘብም በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ለኅብረቱ ሥራ ማስኬጃ የሚውለውን በጀት ሙሉ በሙሉ በአባል አገራት ለመሸፈን ያስችላል ነው የተባለው። በተመሳሳይ ለልማት ሥራዎች ከሚያስፈልገው አጠቃላይ በጀት ውስጥ 75 በመቶና ለሰላምና ፀጥታ ሥራዎች ከሚያስፈልገው በጀት 25 በመቶ ያህሉንም በሀገራቱ የራስ አቅም ለመሸፈን ህብረቱ ውጥን አለው።

የአዲስ አበባው የመሪዎች ጉባዔም በዚህ ዙሪያ ወደ ተግባር ይግባ የሚል ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ሲጠበቅ፤ ቀመሩን እንደ ሩዋንዳው ጉባዔ ሁሉ ተቀብሎ ሲያበቃ ይህ ዓመት የሽግግር ጊዜ ይሁን የሚል ውሳኔን አስተላልፎ ተለያይቷል። ይህ ማለት አሁንም አፍሪካውያን ለአፍሪካዊ አጀንዳቸው ከበለጸጉት አገራት እርዳታ በመለመን ይቀጥላሉ ማለት ነው። ለምን?

አፍሪካውያን በአጀንዳ 2063 የዘመነችና የተረጋጋች አህጉር ለመፍጠር የያዙትን ዕቅድ ማሳካት ካለባቸው አሁንም ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል። በተለይም ኢትዮጵያ በአህጉር ደረጃ ያላትን ታላቅ ታሪክና ለኀብረቱ እዚህ መድረስ በየዘመኑ የከፈለችውን መስዋዕትነት በማስታወስ ይህ ጉዳይ ከዳር ይደርስ ዘንድ ግንባር ቀደም ሆና መታገል አለባት። ታሪካዊው ድርጅት ታሪካዊ ደረጃ ላይ እንዲደርስም ዛሬም ኢትዮጵያ ታሪክ የማይረሳው ትግል ማድረግና ከዳር ማድረስ ይጠበቅባታል።

ይህ ቀመር በተባለው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥም ተግባራዊ ካልሆነ ወይንም ሌላ አማራጭ የወጪ መሸፈኛ መላ ከራሳቸው ከአፍሪካውያን ካልመጣ የኢኮኖሚ ጥገኝነቱ ወደፊትም ይቀጥላል ማለት ነው፤ አፍሪካውያን የሚመኙት የፖለቲካ ነጻነትም «ላም አለኝ …» ሆኖ መቅረቱ ነው። ስለሆነም ቅድሚያ ለአህጉራዊው ተቋም አንፃራዊ የኢኮኖሚ ነፃነት ማለታችንም ለዚሁ ነው።

 

 

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ

 

በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች በሰርቶ ማሳያነት (ፓይለት) መልክ አራት የተቀናጁ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ (አግሮ) ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታቸው ሊጀመር መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር መብራቱ መለስ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ቡሬ፤ በትግራይ ባከር ሁመራ አጠገብ፤ በኦሮሚያ ቡልቡላ እና በደቡብ ክልል ይርጋለም የሚገነቡ ናቸው።

በፓርኮቹ እንደ የአካባቢዎቹ የግብርና ምርቶች ሁኔታ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች እንዲሁም የዶሮና የከብት ሥጋ ፣ የወተት ፣ የማር፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እንደሚቋቋሙ ገልፀው፤ በእያንዳንዱ ፓርክ 60 ትላልቅ ወይም 120 መካከለኛ ፋብሪካዎች እንደሚገነቡም ተናግረዋል፡፡

ለእያንዳንዱ የተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመጀመሪያው ምዕራፍ 50 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክና 600 ሜትር ኪዩብ ውሃ እንደሚያስፈልግም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመው፤ ለአራቱም የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ዝርዝር የአዋጪነት ጥናት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከተባበሩት መንግሥታት ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት እና ከዓለም ምግብ ድርጅት ጋር በመተባበር ማካሄዱን ገልፀዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃም፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ተጠናቆ በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ሲገቡ በአማራ ክልል በቡሬ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያዎች ፓርክ በዓመት 558ሺ ቶን መጠን ያላቸው የተለያዩ ምርቶች ይመረታሉ። ከሽያጫቸውም 14 ቢሊዮን ብር ገቢ ይገኛል። በትግራይ ክልል ከባከር ፓርክ ደግሞ 700ሺ ቶን መጠን ያላቸው የተለያዩ ምርቶች የሚመረቱ ሲሆን፤ ከሽያጩም 18 ቢሊዮን ብር ገቢ የሚገኘ ይሆናል። እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ከቡልቡላ 591ሺ ቶን የተለያዩ ምርቶች እንደሚመረቱና ከሽያጩም ስድስት ቢሊዮን ብር ገቢ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ፡፡

ፓርኮቹ ለ629ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ጠቁመው፤ በአገሪቱ የግብርናና የኢንዱስትሪ ትስስር በማጠናከር የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣትና የህዝቡን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው አስረድተዋል።

 

አየናቸው እሸቱ

Published in የሀገር ውስጥ

ዜና ሐተታ

በኮምቦልቻ ከተማ ላይ በከተማውና በአዋሽ ወልዲያ ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት ዋናው ካምፕ የተገኘነው ማልደን ነበር። የባቡር መስመር ዝርጋታ ክንውንን ሄደን ከመመልከታችን በፊትም በካምፑ የሚመረቱትን የተለያዩ ግብአት ማምረቻዎችንና የምርት ሂደቱን በእይታችን ቃኘን። በዚህ በተንጣለለ የመኖሪያና የስራ ግቢ ውስጥም በርካታ ቱርካውያንና ኢትዮጵያውያን በስራ ተጠምደው ይታያሉ። በወቅቱም ለመረዳት እንደቻልነው፤የፕሮጀክቱ የስራ ክንውን ምዕራፍ ወደ መገባደዱ መቃረቡን ነው።

ፕሮጀክቱ በአንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር "ያፒ መርከዚ" በተሰኙ የቱርክ ተቋራጮች እየተገነባ ይገኛል። በወርሃ ጥቅምት 2007 .ም የተጀመረው ግንባታ አሁን ላይ ከሚዘረጋው 390 ኪሎ ሜትር የሃዲድ ንጣፍ የ150 ኪሎ ሜትሩ መከናወኑን የፕሮጀክቶቹ ሀላፊዎች አስታውቀዋል።

በፕሮጀክቱ የዋሻ ግንባታ ስራ አስኪያጅ የሆኑት ኢንጂነር ድጋፌ ታደሰ፤ የባቡሩ መስመር 12 ያህል ዋሻዎችን እንደሚያቋርጥ ይናገራሉ። በዋሻ ውስጥ የሚሄድ የባቡር መስመር ዝርጋታ እንደ አገር ሲታይ ይህ የመጀመሪያው ነው። በተለይም የዋሻዎቹ ረጅም ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ መሆናቸው ስራውን ፈታኝ አድርጎታልም ይላሉ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በሃብሩ ወረዳ ሁለት ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር በካራ ቆሬ አካባቢ ደግሞ አንድ ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የሚረዝሙና ሌሎች አራት ዋሻዎች ተቦርቡረው የቁፋሮ ስራቸው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቋል። የሃዲድ ንጣፍ ስራቸውም ተከናውኗል።

የድልድይ ስራውን በተመለከተም የፕሮጀክቱ ሴክሽን ማናጀር ኢንጂነር ሻሎም አሹሁሮ፤ ፕሮጀክቱ 65 የድልድይ ስራዎች ያሉት ሲሆን 614 ሜትር ርዝመትና 54 ሜትር ከፍታ ያለው በአንፆኪያ ገምዛ የሚገኘው ድልድይ ረጅሙ መሆኑን ጠቁመዋል። ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ የሃዲድ ንጣፍ ስራው መከናወን ተጀምሯል። መገንባት ካለባቸው ድልድዮችም 35ቶቹ መጠናቀቃቸውንም ኢንጀነሩ አስረድተዋል።

የባቡር ንጣፍ ማምረቻ ኃላፊው ኢንጂነር ኪሩቤል ጥላሁን፤ በበኩላቸው የባቡር መስመሩ ከሚያስፈልገው 730 ሺህ የሃዲድ ንጣፍ ውስጥ እስካሁን 430 ሺህ መመረቱን ይናገራሉ። በቀን ቢያንስ ከአንድ ሺ ያላነሰ የሃዲድ ምንጣፍ እየተመረተ ስለሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉም ይቀርባል። ምርቱ የባቡሩን ሃዲድ የሚሸከም አካል በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚደረግበትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እንደሚመረትም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖርሽን የአዋሽ ወልዲያ ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ስራ አስኪያጂ ኢንጂነር አብዱልከሪም መሃመድ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ ከአሚባራ-ሃይቅ እና ከአዋሽ-ኮምቦልቻ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተካሄደ መሆኑን አውስተዋል። ከአዋሽ-ኮምቦልቻ ያለው ፕሮጀክት አፈፃፀም 66 በመቶ የደረሰ ሲሆን በቀጣይ ነሃሴ ወር መጨረሻ ሙከራ ይደረጋል ብለዋል። የሁለቱም ፕሮጀክቶች አጠቃላይ አፈፃፀም 53 በመቶ መሆኑና በ2011 .ም ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።

ኢንጅነሩ የሲግናሊንግ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የኤሌክትሪክ ምሰሶ፣ የመስኖ ውሃ ማለፊያ እና የሰውና የእንስሳት ማቋራጫ ስራ 38 በመቶ መጠናቀቁንም አንስተዋል። ፕሮጀክቱ ብዙ ውጣ ውረዶችን ቢኖሩትም አጠቃላይ ግንባታው በእቅዱ መሰረት እየተጓዘ መሆኑን አስረድተዋል።

የፕሮጀክቱ አማካሪ ኢንጂነር ጆአኦ ካምፖስ፤ የመሬቱ የመንሸራተት ባህሪ የፕሮጀክቱ አንዱ ፈታኝ ስራ እንደነበር ጠቁመው፤ ስራው ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ስለሚፈለግ የተሰሩ የግንብ ስራዎች ሳይቀሩ ፈርሰው እንዲገነቡ ተደርጓል ብለዋል። በቀጣይም መሬቱ የመንሸራተት ችግር ስላለበት እንዳይከሰት ለማድረግ ድልድዮች በብረት ምሶሶ እየተሰሩ ናቸው። ይህም መሬቱ ክብደትን ለመሸከም ካለው አቅም አኳያ ጥሩ መፍትሄ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃን በጠበቀ መልኩ እየተፋጠነ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የቱርኩ ያፒ መርከዚ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ኢርሀን ሴንግዚ ናቸው።እርሳቸው እንዳሉትም፤ ከግንባታው በተጨማሪ በፕሮጀክቱ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ እያደረጉ በመሆኑ በሰው ኃይል አቅም ግንባታና በቴክኖሎጂ ሽግግር ትልቅ ልምድ እያገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በቀን 27 ሺ ቶን የእቃ ጭነትና አራት ሺህ 320 መንገደኞችን ያጓጉዛል። አንድ የዕቃ መጫኛ ባቡር በአንድ ጊዜ አንደ ሺህ 350 ቶን ሲጭን የሰው መጫኛው ደግሞ 720 ሰዎችን ያጓጉዛል። ይህም በዝቅተኛ ዋጋና በአጭር ጊዜ የተቀላጠፈ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት የአካባቢውን የንግድ ልውውጥና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን እንደሚያነቃቃውም ይጠበቃል።

 

ዳንኤል ዘነበ

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።