Items filtered by date: Friday, 10 February 2017

 

የምርምር ውጤትን ወደ ገቢ ማስገኛነት በመቀየር ተጠቃሚነትን ማስፋት ፤

 

ብዙዎች ስለልጅነት ጊዜያቸው ሲጠየቁ የሚበዛውን ጊዜ በተወለዱበት አካባቢ እንዳሳለፉ ይናገራሉ፡፡ እንደ ዶክተር ሲሳይ ወልደገብርኤል ያሉና  ሰሜን ተወልደው ደቡብ ኢትዮጵያ  ያደጉ ሲያጋጥሙ ደግሞ «ወይ አጋጣሚ» ያሰኛል፡፡ እርሳቸው እንዳጫወቱኝ የተወለዱት ትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ነው፡፡ በወላጆቻቸው ሞት ምክንያት እርሳቸውና ታናሽ እህታቸው ሰብሳቢ ያጣሉ፡፡ በወቅቱ መንግሥት አሳዳጊ የሌላቸውን ልጆች ሰብስቦ በህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ ያሳድግ ስለነበር ዕድሉን አግኝተው ማሳደጊያ ይገባሉ፡፡ ጊዜው 1976ዓም ነው፡፡

 በቅድሚያም ዝዋይ ውስጥ በሚገኘው «አላጌ»የሚባል የህፃናት ማሳደጊያ ነበር የገቡት፡፡ የህፃናቱ ቁጥር ሲጨምር የወታደር ቤተሰብ የሆነና ያልሆኑ ህፃናት እንዲለዩ ተደርጎ እርሳቸው ከእህታቸው ጋር ጋምቤላ በሚገኘው «ድል በትግል የህፃናት ማሳደጊያ»ውስጥ ገቡ፡፡ በማሳደጊያው ከ1977 ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ከቆዩ ኋላ የሥርዓት ለውጥ ተደረገ፡፡ እነርሱንም የኃይማኖት ተቋም ተረክቧቸው፡፡

ዶክተር ሲሳይ በተረከባቸው የኃይማኖት ተቋም ውስጥ ከሦስት ዓመት በላይ አልቆዩም፡፡ አባታቸውን የሚያወቁ ሰው አግኝተው አክሱም ከተማ ተመለሱ፡፡ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ሲመለሱም ከ6ኛ ወደ7ኛ ክፍል ተዛውረው ነበር፡፡ ውጣ ውረድ የበዛበት የልጅነት ህይወታቸው ጥሩም መጥፎም አጋጣሚ ነበረው፡፡መጥፎው አጋጣሚ ታናሽ እህታቸው በእባብ ተነድፋ በሞት ተለየቻቸው፡፡ በማሳደጊያው በልጅነት አብረዋቸው ካሳለፉት ልጆች መለየታቸው ሌላው አሳዛኝ ገጠመኛቸው ነበር፡፡ ህይወታቸው ወዴት እንደሚያመራ አለማወቃቸውም አስጨናቂ ነበር፡፡ የወሰዳቸው ሰው አብሯቸው እንዲኖሩ ቢያደርጉም ትምህርታቸውን ለመቀጠል ቤተክርስቲያን ተጠግተው ከ7ኛ እስከ 12ኛ  ድረስ ተማሩ፡፡ በትምህርታቸውም ጎበዝ ከሚባሉት ተማሪዎች መካከል ይመደባሉ፡፡ የ12ኛ ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን በጥሩ ውጤት አጠናቅቀው ለከፍተኛ ትምህርት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገቡ፡፡

ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ገብተው የመጀመሪያ የትምህርት ምርጫቸው የሆነውን የእንስሳት ህክምና  ደብረዘይት በሚገኘው የእንስሳት ህክምና ተቋም ነበር የተማሩት፡፡ ለትምህርት ምርጫቸው ሞዴል የሆናቸውንም አንድ የእንስሳት ህክምና ማህበረሰብ ጤና መምህር ያስታውሳሉ፡፡ መምህሩ በአሜሪካን አገር ውስጥ አስተማሪ ናቸው፡፡ ክረምት ላይ አክሱም ትምህርት ሲሰጡ ነው ያገኟቸው፡፡ መምህሩንም በጉብዝናቸውም ጭምር ያደንቋቸው ስለነበር እንደርሳቸው ለመሆን ተመኙ፡፡ የልጅነት ምኞታቸው ሰምሮ እንደርሳቸው ለመሆን ቻሉ፡፡

ከስድስት ዓመት የእንስሳት ህክምና ትምህርት በኋላ ወደሥራ ዓለም የገቡት ግብርና ሚኒስቴር ነበር፡፡ የሥራ ቦታቸው ደግሞ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ነበር፡፡ በተመደቡበት ሥራ በተለያዩ ምክንያቶች አልቆዩም፡፡መምህር ሆነው በልጅነታቸው ወደረገጧት ዝዋይ ሄዱ፡፡ ዝዋይ አላጌ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት የህብረተሰብ ጤና  መምህር ሆነው ነበር የተቀጠሩት፡፡ በመምህርነቱም አራት ወራት ብቻ ነበር የቆዩት፡፡የመጨረሻው የሥራ ቦታቸው አሁን ረዳት ፕሮፌሰር ሆነው የሚያገለግሉበት መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ነበር፡፡ ዶክተር ሲሳይ በዩኒቨርሲቲው የህብረተሰብ ጤና መምህርም ናቸው፡፡

ዶክተር ሲሳይ እራሳቸውን ለማበቃትም የሚተጉ ሰው ሲሆኑ፤ በአገር ውስጥና በተለያዩ የውጭ አገራት ተምረዋል፡፡ አጫጭር ስልጠናዎችን በመውሰድ ክህሎታቸውን አሳድገዋል፡፡ ለምርምራቸው የሚያግዛቸው ሀሳብ የሚሰጣቸውን ሁሉ አክብረው ይቀበላሉ፡፡ ከፍተኛ ትምህርት ባለው ሰው ብቻ አያምኑም፡፡ «ትምህርት ከሁሉም ይገኛል» ይላሉ፡፡ በንባብም ወቅቱ በሚጠይቀው የምርምር ሥራ እራሳቸውን ለማብቃት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በምርምር ዘርፉም ሰፊ ተሳትፎ አድረገዋል፡፡ ከምርምር ሥራዎቻቸው መካከልም ወደ16 የሚሆኑት መጽሄቶች «ጆርናሎች» ላይ ለህትመት በቅተዋል፡፡ የምርምር ውጤቶቻቸውም ወደፈጠራ ተቀይረው ገበያ ላይ መውጣት ችለዋል፡፡ ገበያ ላይ ከወጡትም በአንዱ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የወርቅ ሜዳሊያና የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት አግኝተዋል፡፡

ዶክተር ሲሳይ እንዳሉት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ 75 በመቶ ማስተማር፣ ቀሪው ደግሞ ለምርምር ተግባር እና ለማህበረሰብ አገልግሎት ይውላል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን አይቶ ለመፍታት ጥረት ማድረግ፣ ወደ ገቢ ማስገኛነት በመለወጥ የተመራማሪውንና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የማጎልበት ሥራም በመሥራት የምርምር ውጤቶቻቸው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያደርጋሉ፡፡

ምርምራቸውን ወደገንዘብ በመለወጥ የአቅራቢና የተገልጋይ የሁለትዮሽ ተጠቃሚነትን የማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው የሚናገሩት ዶክተር ሲሳይ ገበያ ላይ በተፈለገ ጊዜ የማይገኙና ተገኝተውም ጥቅማቸው እዚህ ግባ የማይባሉትን አሳደው መፍትሄ መስጠት ተቀዳሚ ተግባራቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ «መፍትሄ ለማግኘት ለምን ወደውጭ እናማትራለን» የሚልና ችግርን በራስ የመፍታት ፍለጎታቸውም ከፍተኛ ነው፡፡

ዶክተር ሲሳይ ከምርምር ሥራዎቻቸው መካከል ከሦስት ዓመት በፊት ለህብረተሰብ ጥቅም የዋለው የዶሮ መኖ ይጠቀሳል፡፡ ለምርምራቸው መነሻ የሆናቸው ዶሮዎች የሚጥሏቸው እንቁላሎች ቅርፊት «ሼል» አልባ መሆናቸው ነበር፡፡ በትግራይ ክልል በዶሮ እርባታ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ባደረሷቸው ጥቆማ ነበር ወደምርምሩ የገቡት፡፡ ችግሩ ተከሰተ በተባለበት አካባቢ ምርምር ሲያካሂዱ ዶሮዎቹ በሚመገቡበት ምግብ ውስጥ ንጥረ ነገር አለመኖር ወይም የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘታቸው እንደሆነ ደረሱበት፡፡ ለዶሮዎቹ ተስማሚ የሆነ መኖ በማዘጋጀት ለችግሩ ለተጋለጡ አካባቢዎች ችግር ፈች የሆነ የምርምር ውጤት አገኙ፡፡ በምርምር ግኝታቸው ለመኖ ግብዓት የተጠቀሙበት አንዱ የእንቁላል «ሼል» ቅርፊት ነበር፡፡ ምርምሩ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ግብዓቱን በመሰብሰብ ሥራ ላይ የተሰማሩት ወጣቶች ናቸው፡፡

ሁለተኛው የምርምር ሥራ አንድ ገበሬ ካነሳው ቅሬታ በመነሳት የተሠራ ነው፡፡ አትክልቶችንና ሰሊጥን በሚያጠቃ ተባይ የተቸገረው ገበሬ የተጠቀማቸውን የተባይ ማጥፊያዎች ሁሉ ሲዘረዝርና ምንም እንዳል ፈየዱለት ሲናገር የሰሙት ዶክተር ሲሳይ ሩቅ ሳይሄዱ ከአካባቢ ባገኙት ቅጠላቅጠል ወይም ዕጽዋት ከኬሚካል ነፃ የሆነ ፀረ ተባይ ለተጠቃሚው ማድረሳቸውን አስረድተዋል፡፡ ጎን ለጎንም ለምግብነት የሚውለውን በለስ የተባለውን ፍሬ የሚያጠቃ አደገኛ ትል  ከእጽዋት «የበለስ መዥገር ማጥፊያ»  መድኃኒት በምርምራቸው ይፋ አደረጉ፡፡

 ሌላው የምርምር ሥራ ትኋን ከማደሪያ ክፍሎቻቸው እያስለቀቃቸው የተቸገሩ ተማሪዎቻቸውን ችግር የፈታ ነበር፡፡ የምርምር ግኝቱ እጽዋትን በመጠቀም ጠረን አልባ የትኋን ማጥፊያ መደኃኒት ሲሆን ከጉዳት ሥጋት ነፃና በቀላሉ ተደራሽ ነው፡፡ መድኃኒቱ በተረጨበት ቦታም ተባዮቹ ካሉበት ቦታ ተሰብስበው እንዲመጡ በማድረግ ተባዩን እስከ እንቁላሉ በመግደል ከፍተኛ አቅም አለው፡፡ የምርምር ግኝቱን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም በማረጋገጥ በቅርቡ ተመራማሪውን ዶክተር ሲሳይን የወርቅ ሜዳሊያ እና ማበረታቻ 50ሺህ ብር በመስጠት እውቅና ሰጥቷቸዋል፡፡ ጠረን አልባ የትኋን መድኃኒት ለሽልማት ለውድድር በማቅረባቸው ለሽልማት አበቃቸው እንጂ ሌሎቹም የምርምር ግኝቶቻቸው በኢትዮጵያ አዕምሯአዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ተመዝግበዋል፡፡

መሥሪያ ቤታችን ድረስ መጥተው ስለፈጠራ ሥራቸውና በህይወታቸው ዙሪያ ያጫወቱን ዶክተር ሲሳይ መንፈሰ ጠንካራ ሆነው ነው ያገኘናቸው፡፡ ያለቤተሰብ ድጋፍ አሁን የደረሱበት ደረጃ መድረሳቸው ብቻ ሳይሆን በተሰማሩበት የምርምር ሥራም «ተመራማሪው የታለ» ብሎ መንግሥት እንዲፈልጋቸው እንጂ መንግሥት ድጋፍ እስኪያደርግላቸው አይጠብቁም፡፡ አብዛኛውን የምርምር ሥራዎቻቸውን በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እንደሚያከናውኑ ነው የገለጹልን፡፡ አፈርና ውሃ ሳያስፈልገው በ7 ቀናት ውስጥ አረንጓዴ የእንስሳት መኖ ለማብቀልም በምርምር ላይ ይገኛሉ፡፡ ፈረሶችን እያቆሰለ ለከፋ የጤና ችግር ለሚያጋልጣቸውም መፍትሄ በምርምር ለማግኘት በሙከራ ላይ ናቸው፡፡

 

ለምለም መንግሥቱ

Published in ማህበራዊ

የኢትዮጵያ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በተከታታይ ያለፉ ውጤቶችን እና ቀጣይ ጨዋታዎችን እየጠቆምናችሁ ቆይተናል። አሁን ሊጉ የመጀመሪያውን 15ዙር ጨዋታዎች አጠናቋል። ጥቂት ቀናቶችን እረፍት አድርጎ ሁለተኛውን ዙር ይጀምራል። ሊጉ በጣም ጠንካራ ፉክክር ተደርጎበታል ማለት ባያስደፍርም፤ ነገር ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አዳማ ከተማ እንዲሁም ደደቢት የደረጃውን አናት በተደጋጋሚ ጊዜ እየተፎካከሩ መርተውታል። በመጀመሪያው ዙር የተመዘገበው ከፍተኛ ነጥብ በቅዱስ ጊዮርጊስ የተገኘ ሲሆን፣ ደረጃውን በ29 ነጥብ እየመራ መጨረስ ችሏል።

ደደቢት እና አዳማ ከተማ 27 እና 26 ተቀራራቢ ነጥብ በመያዝ የአንደኛውን ዙር ጨዋታ አገባደዋል። ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያው ዙር የውጤት ቀውስ ቢገጥመውም ባለቀ ሰዓት ደረጃውን አሻሽሎ፤ ከሲዳማ ቡና አንድ ደረጃ ዝቅ ብሎ  አምስተኛ ላይ  መምጣት ችሏል። ሆኖም ግን ፋሲል ከተማ ከወላይታ ድቻ በሚያደርጉት ጨዋታ፤ ፋሲል ሙሉ ሦስት ነጥብ የሚያገኝ ከሆነ የደረጃ ለውጥ የሚኖር ይሆናል (የዝግጅት ክፍላችን ለህትመት እስከገባ ድረስ የውጤቱን ሪፖርት ማወቅ አልቻለም)። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሀዋሳ ቀሪ ጨዋታቸውን አድርገዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የላከልን መረጃ እንደሚያመለክተው የ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ወንዶች ፕሪሚየር ሊግ 1ኛ ዙር የውድድር አፈፃፀም ግምገማ የካቲት 7 ቀን 2009 ዓ.ም ከጠዋቱ በ2፡30 ጀምሮ በወላይታ ሶዶ ከተማ፤ በአበበ ዘለቀ ኢንተርናሽናል ሆቴል የሚካሄድ መሆኑን ለማወቅ ችለናል። የሊግ ኮሚቴው  ግምገማውን እንዳደረገ የሚነሱ ጉዳዮችን ይዘንላችሁ ለመቅረብ እንሞክራለን።

ፌዴሬሽኑ በተመሳሳይ የ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 1 ዙር የውድድር አፈፃፀም ግምገማ ትናንት ከጠዋቱ በ2፡30 ጀምሮ በአዳማ ከተማ በየባ ኢንተርናሽናል ሆቴል ማድረጉን  የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

 

ዳግም ከበደ

Published in ስፖርት

 

አሁን ላይ እግር ኳስ ማህበራዊ፣ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው በእጅጉ እየጨመረ ነው። ከሁለት ባላጋራዎች የሜዳ ላይ ፉክክር አልፎ እያንዳንዳችን ቤት ገብቷል። ከሌሎች ስፖርታዊ ክንውኖች ባሻገር ዓለም አቀፍ ተፅዕኖውም በጣም ከፍተኛ ነው። ክለቦች፣ ብሔራዊ ቡድኖች እንዲሁም የእግር ኳስ አካዳሚዎች ረብጣ ገንዘብ በስፖርቱ ላይ በማፍሰስ የድል ማማ ላይ ለመንጠልጠል ይፎካከራሉ። ማንኛውንም ነገር ስኬት ላይ የሚያደርሳቸው ከሆነ ያለማቅማማት ተግባራዊ ያደርጉታል።

ድሮ ድሮ የእግር ኳስ ቡድኖች ተጫዋቾቻቸውን በታክቲክ እና በአካል ብቃት እንዲሁም በተለያዩ የተግባር ልምምዶች ይገነቡ ነበር። በዚህ ዘመን ግን በውድድሮች ሁሉ አሸናፊ ለመሆን እርሱ ብቻ በቂ ሆኖ አልተገኘም። የተጫዋቾች የስነ ልቦና ይዘት እና ያሉበት ሁኔታ ለአንድ ቡድን ማሸነፍ ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ ነው። በመሆኑም ያላቸውን አቅም እና ክህሎት በሚገባ እንዲጠቀሙበት፤ በራስ መተማመናቸው እና የስነ ልቦና ይዞታቸው ጥሩ ሁኔታ ላይ መገኘት ይኖርበታል። ምንም እንኳን አንድ እግር ኳስ ተጫዋች የአካል ብቃቱ እና የታክቲክ ክህሎቱ ጥሩ ሁኔታ ላይ ቢገኝም፤ በተለያየ ምክንያት የስነ ልቦናው ይዞታው ጥሩ ካልሆነ በሚፈለገው ደረጃ የሚጫወትበትን ቡድን ሊጠቅም አይችልም። ይህ በመሆኑ የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድኖች፣ክለቦች እንዲሁም አካዳሚዎች የተጫዋቾቻቸውን የስነ ልቦና ደረጃ በመልካም ሁኔታ ለማሳደግ በዘርፉ ጠበብት የሆኑ ባለሙያዎቻቸውን በቡድናቸው ውስጥ ያካትታሉ።

ለዛሬ የዝግጅት ክፍላችን «ስነ ልቦና በእግር ኳስ መድረክ ላይ ያለው ጠቀሜታ»ን ለመዳሰስ ይሞክራል። በተለይም በአገራችን የእግር ኳስ ዕድገት ላይ የስነ ልቦና ሳይንስ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር፤ የስፖርቱ ቤተሰቦች ይህንን ተግባራዊ እንዲያደርጉ አንዳንድ ነጥቦችን ለመጠቆም ይሞክራል። በዚህ ወቅት ብሄራዊ ቡድናችን እንዲሁም በአገሪቷ የሚገኙ ክለቦች፤ የስነ ልቦና ሳይንሱን በሚገባ ተረድተው ከጥቅሞቹ ለመቋደስ መሄድ የሚገባቸውን ርቀት እንዳልተጓዙ የሚያመለክቱ በርካታ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል። ሆኖም ለምን ተግባራዊ አላደረጉም የሚል ትችት ከመሰንዘር ባለፈ ዘርፉ ያለውን ጠቀሜታ ለመዳሰስ እና  ጉልህ ሚናውን ለነዚህ የስፖርት ቤተሰቦች ለማሳየት እንሞክራለን። ይህ ዳሰሳ ስነ ልቦናን ከእግር ኳስ አንፃር ቢቃኝም ቅሉ ሳይንሱ ለሌሎች ስፖርቶች አይሰራም ማለት እንዳልሆነ ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል። መልካም ንባብ!!

የእግር ኳስ ደረጃቸው ጫፍ ላይ የደረሱ ብሄራዊ ቡድኖች እና ክለቦች በስብስባቸው ላይ የተጫዋቾቻቸውን ስነ ልቦና ደረጃ ከፍ ለማድረግ፤ በሳይንሱ ብቁ ቦታ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎችን በቡድናቸው ውስጥ ያካትታሉ። የስነ ልቦና ህክምና ወይም ድጋፍ በአውሮፓ የእግር ኳስ ቡድኖች ውስጥ የሚካተት ቢሆንም   በስፋት ግን የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት አያገኝም። ምክንያቱም በባህሪው ለተጫዋቾች የሚደረገው የስነ ልቦና ድጋፍ ምስጢራዊ ይዘት ስለሚኖረው ነው። ሆኖም ግን ተጫዋቾች ከተለመደው ልምምዳቸው እኩል የስነ ልቦና ድጋፍ ሲያስፈልጋቸው ጎን ለጎን መውሰዳቸው አዲስ አይደለም።

ዶክተር ቲም ኦብሪን በዘርፉ ከፍተኛ ዝናና አድናቆትን ያተረፉ የስነ ልቦና ባለሙያ ናቸው። በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በርካታ ደጋፊ እና አስደናቂ ክብረ ወሰኖች ባለቤት ከሆነው አርሰናል ክለብ ጋር ከ10ዓመት በላይ አብረው ሰርተዋል። እኚህ አንጋፋ የዘርፉ ጠቢብ በአርሰናል ቤት አሻራቸውን ጥለው ላለፉት ዴኒስ ቤርካምፕ፣ሮበርት ፒሬዝ፣ቴሪ ዳንኤል ሄንሪ እና ሌሎች ተጫዋቾች እርዳታ ባስፈለጋቸው ቁጥር ከጎናቸው ነበሩ። ዶክተሩ «የስነ ልቦና ህክምና» ለእግር ኳስ ያለውን ከፍተኛ ጠቀሜታ ይናገራሉ።

ዶክተር ቲም በስነ ልቦናው ሳይንስ «እሳቤ፣ስሜት እና ባህሪ» ያላቸውን የተወሳሰበ ግንኙነት ትኩረት በማድረግ ይሰራሉ። እነዚህ ሦስት አስፈላጊ ነገሮች ሲሆኑ በተጫዋቾች ብቃት ላይ በአሉታዊ እና አወንታዊ መልኩ ተፅዕኖ ያሳድራሉ። ባለሙያው ተጫዋቾቹ ያላቸውን ትክክለኛ አቅም አውጥተው እንዲጠቀሙ፤ ስሜት፣ባህሪ እና እሳቤያቸው ጤናማ ግንኙነት እንዲያደርጉ እርዳታቸውን ይለግሷቸዋል። በእግር ኳስ ክለቦች የስነ ልቦና ባለሙያ ቀጥሮ ድጋፍ ማድረግ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። እንደ ዶክተር ቲም ገለፃ ግን በእግር ኳስ ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሰው ልጅ እሳቤ የዚህ ሳይንስ ድጋፍ ጠቀሜታ የትዬለሌ ነው።

«እኔ በስፖርት ውስጥ የምሰራ የስነ ልቦና ባለሙያ እንጂ፤ የእግር ኳስ ስነ ልቦና ባለሙያ አይደለሁም። እኛ እያወራን ያለነው ስለ ሰው ልጆች ነው። ስለዚህ ሁሉም እሳቤውን እና አዕምሮውን በጥልቅ እንዲገነዘብ ማድረግ ተገቢ ነው። በጥልቅ አዕምሯችን ውስጥ ያለው ታሪክ እሳቤያችንን፣ስሜታችንን እና ድርጊታችንን ይመራዋል። ሁላችንም በአዕምሯችን ውስጥ የተለያየ ጥልቅ ታሪክ አለን። ስለዚህ ይህ ታሪካችን እኛነታችንን እንዴት እንደሚገድበን እና እንደሚቀይረን መረዳት መቻል ይኖርብናል። አብዛኛው የስፖርት ቤተሰብ ተጫዋቾችን እንደ ቴአትረኛ ይመለከታቸዋል። ነገር ግን የእግር ኳስ ቴአትረኛ ከመሆናቸው በፊት ሰዎች ነበሩ» በማለት ዶክተር ቲም የተጫዋቾችን ጥልቅ ስሜት፣እሳቤ እና ባህሪ በመረዳት ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚረዷቸው ይናገራሉ። የብቃታቸው ጫፍ ላይ የደረሱ ተጫዋቾች ቢኖሩ  እንኳን የስነ ልቦና ጥንካሬያቸው በዚያን ወቅት ጥሩ ካልሆነ በፈለጉት ደረጃ ቡድናቸውን መጥቀም አይችሉም። የአጠቃላይ ቡድኑ ጥንካሬ በእነርሱ ወቅታዊ ብቃት ላይ የተመሰረተ ነው፣ በማለት በተለያዩ ጉዳዮች የእግር ኳስ ተጫዋቾች የስነ ልቦና ችግር ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ይናገራሉ። በዚህ ጊዜም ከባለሙያ ድጋፍ ማግኘት እንደሚኖርባቸው ይጠቁማሉ።

አንድ አግር ኳስ ተጫዋች 90 ደቂቃ ሊጫወት ይችላል። እግር ኳስ የታክቲክ፣ የሰውነት ንክኪ እና የፈጠራ ብቃት ላይ የተመሰረተ ጨዋታ ነው። ነገር ግን ይህ ጨዋታ የስነ ልቦና ቁማርንም «psychological game» እንደሚጨምር መረዳት ይኖርብናል። ወደ አገራችን ስንመለስ በተለያዩ ክለቦች እና ፕሮጀክቶች በርካታ ተጫዋቾች አሉ። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የአገራችንን ክለቦች ስንመለከት ለቡድናቸው አስፈላጊውን ሁሉ በማሟላት ቡድናቸውን ውጤታማ ለማድረግ ሙሉ አቅም ላይኖራቸው ይችላል። ነገር ግን ለስኬታቸው ቁልፍ የውጤታማነት መሰረት የሆኑ ጉዳዮችን መረዳት እና መተግበር ይኖርባቸዋል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ተጫዋቾቻቸውን በስነ ልቦና ሳይንስ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ባለሙያዎችን በቡድናቸው ውስጥ ማካተት ቀዳሚው ተግባር ነው።

ዶክተር ቲም ከላይ ያነሳነውን ጉዳይ የሚያጠናክር ሃሳብ ያነሳሉ «ለምሳሌ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ያሉ ተጫዋቾችን እንመልከት። ሊጉ በጣም ፍጥነት የተቀላቀለበት ነው። ተጫዋቾቹ በዚያ ሁኔታ ላይ ሆነው እንኳን በጣም አስደናቂ ሁኔታዎችን በሰከንድ ውስጥ ሲወስኑ እና ሲተገብሩ እንመለከታለን። ከቡድናቸው ጋር በቀላሉ መናበብ ይችላሉ። በሙሉ የራስ መተማመን እና ጥንካሬ ከተፋላሚያቸው ጋር ይፋጠጣሉ። ይህ እንዲሆን ከተፈለገ አንድ የእግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾቹን የሚደግፍ፣የሚያበረታታ እንዲሁም ጭንቀታቸውን እና የአዕምሮ ውጥረታቸውን የሚያስወግድ የስነ ልቦና ባለሙያ ያስፈልገዋል» ሲሉ አስተያየታቸውን ያስቀምጣሉ።

እግር ኳስ  በጣም በርካታ ተመልካች ባለበት ሜዳ ላይ ለ90 ደቂቃዎች የሚደረግ ፍልሚያ ነው። ከዛም ባለፈ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ሰፊ ሽፋን ያገኛል። በተለይ አሁን የማህበራዊ ድረ ገፆች መስፋፋትን ተከትሎ በእያንዳንዷ ሰከንድ ከተጫዋቾች እና ከክለቦች ጋር የተያያዙ መረጃዎች ይወጣሉ። በበጎም ሆነ በመልካም ነገር የሚዛመት የተጫዋቾች መረጃ ለስነ ልቦና ጫና ያጋልጣል። ይህ ደግሞ የተጫዋቾቹን የግል ህይወት ሲጨምር ጫናው እንዲበረታ ያደርገዋል። በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው።

የስነ ልቦና «ጫና» እና «ውጥረት» የየራሳቸው ባህሪ አላቸው። በእግር ኳስ አምጥተን ከተመለከትናቸው ደግሞ፤ አንዳንዶቹ ተጫዋቾች በጫና ውስጥ ሆነው ጥሩ ብቃታቸውን ሊያሳዩ ይችላሉ። ጫናውን ይወዱታል። ምክንያቱም በእያንዳንዷ ጨዋታ ላይ ያዳበሩት ልምድ እንዲቋቋሙት አስችሏቸዋል።

ዶክተር ቲም ሲናገሩ « በህይወት ውስጥ ጫና ወደ ውጥረት ሲቀየር፤ ነገሮችን ለመቋቋም የሚያስችል የስነ ልቦና ብቃት እንደሌለህ ልታስብ ትችላለህ።ይህ በስፖርቱ ዘርፍ ላይ ተመሳሳይ ነው። በዚህ ጊዜ እርዳታ ያስፈልግሀል። የባለሙያ እርዳታ ደግሞ በጫና ውስጥ ሆነህ እንዴት ስኬታማ እንቅስቃሴ እንደምታደርግ መንገዱን ያመላክትሀል» በማለት በእግር ኳስ ህይወት ላይ ምን ያህል ህክምናው ጠቀሜታ እንዳለው ለማስረዳት ይሞክራሉ።

የሰው ልጅ አዕምሮ ውስብስብ እና በጣም ምስጢራዊ አሰራር ያለው ነው። ይህ በመሆኑ በስነ ልቦና ህክምና ላይ ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችን በሥራዎቻችን ላይ ማሳተፍ ለውጤታማነታችን አሌ የማይባል አስተዋፅኦ ያበረክታል። በእግር ኳስ ዘርፉ ላይ የስነ ልቦና ባለሙያዎችን በቡድናቸው ውስጥ ከሚያካትቱት ውስጥ እንደ ምሳሌ ከላይ ያነሳነው የእንግሊዙን አርሰናል ክለብ ነው። በአሁኑ ሰዓት ክለቡ በቦርዱ ውስጥ ዶክተር ሴሪ ኢቫንስን አካቷል። እርሳቸው የስነ አእምሮ ባለሙያ ናቸው። በስኬታማነት ከሚጠቀስላቸው ሥራ መካከል የሲውዘርላንድ የራግቢ ብሄራዊ ቡድንን በሙያቸው እየረዱ የዓለም ዋንጫ ማንሳት መቻላቸው ነው። ከዚህም ሌላ በዋናው ቡድን ላይ የስነ ልቦና እና የስነ አዕምሮ ማበልፀጊያ ክፍል ኃላፊው ዴቪድ ፕሪስትሊ ይገኛሉ።

የእግር ኳስ ቡድኖች የሙሉ ጊዜ የስነ ልቦና ባለሙያ ለመቅጠር የሚገደዱት ስፖርቱ በተጫዋቾች ላይ ይዞት የሚመጣው ውስብስብ ተፅዕኖ ስላለ ነው። ነገር ግን የእግር ኳስ ቡድን ስንል ምን ማለታችን ነው? የእግር ኳስ ቡድን በአንድ መንደር ወስጥ እንደሚኖሩ እና በጥብቅ ማህበራዊ ግንኙነት እንደተሳሰሩ ማህበረሰቦች ይመሰላል። ዝም ብሎ 11 ተጫዋቾች ከሌላ ባላጋራቸው ጋር በሜዳ ላይ የሚያደርጉት ፍልሚያ አይደለም። በጨዋታው ለማሸነፍ በሜዳ ላይ ብቻ አብሮ መግባት በቂ አይደለም። ከዚህ ሌላ ቡድኑ አሸናፊ ለመሆን የአይበገሬነት እና በጣም የጠነከረ አንድነት ሊኖረው ይገባል። ይህ ሲሆን የሚፈለገው ውጤት ይመጣል። አንድ ተጫዋች የራሱ ማንነት እና ጥንካሬ ሊኖረው ይችላል። አንድ ቡድንም እንዲሁ በተመሳሳይ የራሱ ማንነት፣ ጥንካሬ እንዲሁም ድክመት ይኖረዋል። በአንድ ቡድን ውስጥ ያሉ ተጫዋቾች ደግሞ የተለያየ ማንነት፣ባህል፣ ብቃት እንዲሁም የስነ ልቦና ጥንካሬ ላይ የሚገኙ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህን ሁሉ  የተሟላ እና ጥሩ በሆነ የራስ መተማመን አሸናፊነትን እንዲላበሱ፤ እንደነ ዶክተር ቲም ያለ የስነ ልቦና ሳይንስን ጠንቅቆ የሚያውቅ ባለሙያ ቡድኑ ሊኖረው ይገባል።

  ዶክተር ቲም መጀመሪያ ከእግር ኳስ ተጫዋቾች ጋር መስራት ሲጀምሩ ያጋጠማቸውን ነገር ሲገልፁ እንዲህ ይላሉ «ልክ ሥራዬን ስጀምር በአብዛኛው እግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ አንድ ድምዳሜ ነበር። ይሄም አንዳንድ ተጫዋቾች በስነ ልቦና ደካማ አንዳንዶቹ ደግሞ ጠንካራ አድርጎ የመውሰድ የተሳሳተ አመለካከት ነበር። በስነ ልቦና ባለሙያ የሚረዱ ተጫዋቾች በደፈናው ደካማ እንደሆኑ ይቆጠር ነበር። ይህ ግን ፍፁም የተሳሳተ ነው። የስነ ልቦና ባለሙያ ከነበረህ ጥሩ አቋም የተሻለ ጥንካሬ እና ብቃት እንድትጨምር ያግዛል እንጂ፤ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ብቻ ህክምና አያደርግም» በማለት የአዕምሮ ደካማነት «mental weakness» እንዲሁም የአዕምሮ ጥንካሬ «mental strength» ፤ በምርምር ላይ ተመስርቶ በሚገኝ ውጤት የሚረጋገጥ እንጂ በደፈናው አንድ ተጫዋች በስነ ልቦና ባለሙያ ስለተደገፈ እና ስላልተደገፈ የሚታወቅ አለመሆኑን ያስረዳሉ። ባለሙያው በቡድን ውስጥ በዋናነት የሚያስፈልገውም ቀለል ያሉ ማህበራዊ እና ግላዊ ችግሮችን በመቅረፍ ውጤታማነትን ስለሚያጎናፅፍ መሆኑን ይገልፃሉ።

በቅርቡ የእግር ኳስ ተጫዋቾች የስነ አዕምሮ ይዞታ መሰረት አድርጎ የወጣ «ፊፍ ፕሮፕ» የተባለ ጥናት እንደጠቆመው በአሁኑ ሰዓት በዓለም ዙሪያ ላይ እየተጫወቱ ከሚገኙ 607 ተጫዋቾች (ጥናቱን ለመስራት ከተመረጡት) ውስጥ 38 በመቶ የሚሆኑት፤ እግር ኳስን ተጫውተው ካለፉ 219 ተጫዋቾች ደግሞ 35 በመቶ የሚሆኑት፤ በጭንቀት፣ ጥልቅ በሆነ ድብርት እንዲሁም ውጥረት የተጠቁ መሆኑን አረጋግጧል። ሌላ ተጨማሪ ማረጋገጫ እና አስተያየት ሳንጠብቅ፤ የጥናቱ ውጤት ላይ ብቻ ተመስርተን ምን ያህል የስነ ልቦና ባለሙያ በእግር ኳስ ቡድን ውስጥ አስፈላጊ መሆኑን መገመት አያቅተንም።

ዶክተር ቲም «ስሜትህ ሁል ጊዜ ዓለምን በምትረዳበት ልክ ነው የሚሆነው። ለምትሰራው ሥራ ዋጋ የምትሰጥ ከሆነ ያ በእርግጠኝነት ደስተኛ ያደርግሀል። ይህን ለመረዳት ደግሞ የባለሙያ እገዛ ያስፈልግሀል። ምንም ሥራ ምን የመጨረሻ ግብ ሊኖርህ ይገባል። የእግር ኳስ ደረጃቸው በጣም ከፍተኛ በሆነ አገር ውስጥ ረብጣ ገንዘብ እየተከፈለህ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ፍላጎትህን፣ ስሜትህን እንዲሁም አስተሳሰብህን ሊከፋፍል የሚችል ጉዳይ ከገጠመህ ደስታህን ይነጥቀዋል። ይሄ ደግሞ በአቋምህ እና ወቅታዊ ብቃትህ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል» በማለት ይናገራሉ። ይህ በሚሆን ሰዓት ደግሞ ቡድኑን ለመርዳት አብረው የሚገኙ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ትልቁን ሚና ይጫወታሉ በማለት ዶክተር ቲም ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ሰፊ ርቀት መጓዝ አይጠይቅም። ለዕድገቱ መጓተት ብሎም ባለበት ደረጃ ላይ መቆም፤ በርካታ ምክንያቶች ይነሳሉ። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ በዋናነት እግር ኳሱ ዘመኑ ከፈቀደው የስልጣኔ እና ቴክኖሎጂ ትሩፋት ለመቋደስ ባለመቻሉ መሆኑን የተለያዩ ባለሙያዎች በየፊናቸው ይናገራሉ። እኛም ይህንኑ መነሻ በማድረግ ነው የዛሬውን ዘገባችንን ከአካላዊ እንቅስቃሴ ውጪ ባለው የእግር ኳስ ስነ ልቦና ላይ ማተኮር የፈለግነው። በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ዳሰሳውን በያዘው የመረጃ ልክ ተገንዝበውት ወደዚህ አሰራር ቢገቡ አንድ እርምጃ ወደፊት መጓዝ ይችላሉ የሚል እሳቤ አለን። ሰላም!

 

ዳግም ከበደ

Published in ስፖርት
Friday, 10 February 2017 18:16

ሳምንቱ በታሪክ

 • ጥር 29/1780 ዓ.ም - ማሳቹሴትስ የአሜሪካን ሕገ መንግሥት የፈረመች ስድስተኛዋ የአሜሪካ ግዛት ሆነች፡፡
 • ጥር 29/1934 ዓ.ም - በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ብሪታኒያ በታይላንድ ላይ ጦርነት አወጀች፡፡
 • ጥር 29/1950 ዓ.ም - ስምንት የማንቸስተር ዩናይትድ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾችና አስራ አምስት ተሳፋሪዎች በሙኒክ የአውሮፕላን አደጋ ህይወታቸውን አጡ፡፡
 • ጥር 30/1787 ዓ.ም - የምክትል ፕሬዝዳንቱ ሥልጣን ላይ ማስተካከያዎችን ያደረገው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት አስራ አንደኛው ማሻሻያ ፀደቀ፡፡
 • የካቲት 1/1829 ዓ.ም - ሪቻርድ ጆንሰን በዩናይትድ ስቴትስ ሴኔት የተመረጡ •የመጀመሪያው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኑ፡፡
 • የካቲት 1/1848 ዓ.ም - የቋራው ካሳ ኃይሉ በአቡነ ሰላማ እጅ ተቀብተው ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በመባል በደረ ጽጌ ማርያም ቤተ-ክርስቲያን ነገሡ፡፡
 • የካቲት 1/1914 ዓ.ም - የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዋረን ኸርዲንግ የመጀመሪያውን የራዲዮ ጣቢያ በዋይት ሃውስ አስተከሉ፡፡
 • የካቲት 1/1944 ዓ.ም - ኤልሳቤጥ ሁለተኛ የታላቋ ብሪታኒያ ንግሥት ተብለው ነገሡ፡፡
 • የካቲት 2/1951 ዓ.ም - አር-7 ሰሚዮርካ (R-7 Semyorka) የመጀመሪያው አህጉር ተሻጋሪ ባሊስቲክ ሚሳይል ሆኖ በተባበሩት ሶሻሊስት ሶቭየት ኅብረት (USSR) ጥቅም ላይ ዋለ፡፡
 • የካቲት 3/1862 ዓ.ም - የወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (Young Women Christian Association - YWCA) ተመሰረተ፡፡
 • የካቲት 4/1786 ዓ.ም - የአሜሪካ ሴኔት ስብሰባ ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝብ ክፍት ሆነ፡፡
 • የካቲት 4/1930 ዓ.ም - ቢቢሲ የቴሌቪዥን ጣቢያ በዓለም የመጀመሪያውን ሳይንሳዊ ልብ ወለድ ፕሮግራም ሠርቶ አቀረበ፡፡
 • የካቲት 4/1947 ዓ.ም - ሶቭየት ኅብረት ከእስራኤል ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋረጠች፡፡
 • የካቲት 4/1982 ዓ.ም - የደቡብ አፍሪካው የነፃነት ታጋይና መሪ ኔልሰን ማንዴላ ከቪክቶር ቨስተር እስር ቤት ተለቀቁ፡፡

 

አንተነህ ቸሬ 

 

Published in መዝናኛ

 

ከ155 ዓመታት በፊት በዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት እንዲህ ሆኖ ነበር፡፡ የመስቀል በዓል በዋለ በሁለተኛው ቀን በዓሉን ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቁንጅና ውድድር በጎንደር ከተማ ተደርጎ ነበር፡፡ ከልደታ ምስራቅ ለአበራ ጊዮርጊስ ሰሜን ከሆነችው በቀሃ ወንዝ አጠገብ ከምትገኘው አጤ ሰቀላ ኮረብታ ላይ የንጉሠ ነገሥቱ ድንኳን ተተከለ፡፡  

ከጧቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ የከተማውና የአገሩ ህዝብ በዓሉ ወደሚከበርበት ሜዳ ይጎርፍ ጀመር፡፡ አራት ሰዓት ሲሆን ምርጥ መሳሪያ የያዙ ወታደሮችና አጋፋሪዎች ሰልፈኛውን ለማስተናበርና ፀጥታውን ለማስከበር በበዓሉ ሜዳ ተሰማሩ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ፊታውራሪ ገብርዬ በሠራዊቱ ታጅቦ ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለበ አጤ ሰቀላ ደረሰና የዙፋኑን አቀማመጥ ተመለከተ፡፡

እንዲሁም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ በፈረሶች በሚሳብ ሰረገላ ላይ ተቀምጠው ሊቀ መኳስ ዮሐንስ ቤል ባሰለጠናቸው ወታደሮች ታጅበው መጥተው በዙፋናቸው ላይ እንደተቀመጡ እምቢልታና መለከቱ ተብላላ፡፡ ለውድድሩ የታጩት ወይዛዝርት ጥልፍ ቀሚሳቸውን እያንሰረተቱ፣ ተቀብለውና ተኳኩለው ወደ ተዘጋጀላቸው ቦታ ያልፋሉ፡፡

ቀጥሎም ምርጫው በሚፈፀምበት ጎል እየገቡ ውበታቸውና ደም ግባታቸው፣ የላሕየ ገፃቸው አወራረድ፣ የፀጉራቸው ስሬት፣ የቁንዳላቸው ርዝመት፣ ሽንጣቸው፣ ዳሌያቸውና ተረከዛቸው እየተመረመረ የምርጫው ስነ ስርዓት ይጀመራል፡፡ በመካከሉ ከሰቀልት ወረዳ ከመቋሚያ ማርያም የመጣችው ትውልዷ ከመቄት ዘእማቾች ወገን የሆነች የደጃዝማች ይልማ አሰፋ ልጅ፣ ጣይቱ ይልማ አንደኛ ስትሆን፣ እንዲሁም ከጎንደር አዲስ ዓለም የመጣችው የመሐመድ ኩርማን ሚስት የሼህ መሀመድ ጌታ ልጅ ተዋበች በፀጉሯ ማማር፣ በቁንዳላዋ አወራረድና መርዘም ሁለተኛነትን አግኝታለች፡፡

ከዚህ በኋላ ፊታውራሪ ገብርዬና ሊቀ መኳስ ዮሐንስ ቤል የምርጫውን ውጤት ለንጉሠ ነገሥቱ ለመንገር ወደ ዙፋኑ ይቀርባሉ፡፡ ወዲያውም ጣይቱ ይልማ አንደኛ እንዲሁም ተዋበች መሀመድ ጌታ ሁለተኛ መሆናቸውን ከገለፁ በኋላ ተመራጮቹ ከዙፋኑ ፊት በመቅረብ እጅ እየነሱ ሽልማታቸውን ተቀብለው የበዓሉ ፍፃሜ ሆኖ በሰባት ሰዓት እንደተለመደው ለመሳፍንት፣ ለሊቃውንት፣ ለመኳንንትና ለካህናት የምሳ ግብዣ ተደረገ፡፡ ከውድድሩ በኋላ ኦርማኤል (ወርመር) የተባለው በጋፋት የመድፍ ሠራተኞች አለቃ አንደኛ የወጣችውን ጣይቱ ይልማን በሚስትነት አግብቶ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወልደዋል፡፡ ጋይንት ውስጥ አሁንም በኦርማኤል ስም የሚጠራ መሬት አለ፡፡

(ምንጭ፡ ዕንቁ መጽሔት ጥቅምት 2004 ዓ.ም (ከገሪማ ታፈረ - የቋራው አንበሳ አባ ታጠቅ ካሳ)

 

አንተነህ ቸሬ

Published in መዝናኛ
Friday, 10 February 2017 18:13

የመተኛት ቀን ወይንስ...

 

       እርስዎ አለባበስዎን ለማሳመር ብለው ያደረጉት የቀለም ምርጫ ሳያስቡት ትርጉም እንዳያሰጥብዎት፡፡ ይህ ጥንቃቄ ለሰሞኑ ብቻ ነው፡፡ አልባሳትና ጌጣጌጥ ነጋዴዎች ካለቀይ ቀለም አልታይ ብሏቸዋል፡፡ በደጃፎቻቸው ላይ ጎላ ባለ ጽሁፍ የለጠፉት የጎብኙን ጥሪ እንኳን ሳይቀር በቀይ ቀለም የተጻፈ ነው ፡፡ በከተማዋ የሚታየው የዚህ የቀይ ቀን ንቅናቄ በሌሎች ቀን ላይ አይጎላም፡፡ መገናኛ ብዙሃን እንኳን ሳይቀሩ ቀኑን ያራግቡታል፡፡የእናቶች፣ የሴቶች፣ የአባቶች እና የሌሎችም በርካታ የሚከበሩ ቀናት እንደዚህ  ወቅት በሰው ጆሮ አይደርሱም፡፡

     ትናንት በታክሲ ትራንስፖርት ስሄድ ያጋጠመኝን ልንገራችሁ ከጎኔ አንድ ሴትና አንድ ወንድ ልጅ ተቀምጠዋል፡፡ ወንዱ በአንድ ህንጻ ሥር በሚገኝ የንግድ ሱቅ ላይ በቀይ ቀለም ጎላ ባለ የንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈ ያሳያታል፡፡ አልተ ረዳችውም ፡፡ « ዳሩ ቦይፍሬንድ የለሽም» አላት፡፡ ጽሁፉ «ቫላንታይን ዴይ» ይላል፡፡ የምናውቀው የፍቅረኛሞች ቀን ሲባል ነው፡፡ ገና ቀናት ለቀሩት ለዚህ የቀይ ቀን ቀድሞ የተጀመረው ጥሪ መልዕክት ለሁሉም  ግልጽ ሆኖ ይሆን? ጥያቄ ስለፈጠረብኝ ነው ይህን ጉዳይ ማንሳቴ፡፡ ቀኑ አንዳቸው ለሌለኛቸው ፍቅራቸውን የሚገልፁበት ሳይሆን የሚተኙበት ቀን እስኪመስል ነው ቅስቀሳ የሚደረገው፡፡ ቀኑን በተመለከተ በየመገናኛ ብዙሃኑ ደምቀው የሚተላለፉት ማስታወቂያዎችም ይህንኑ የሚያበረታቱ ናቸው፡፡

        እንዳልኩት የመተኛት ቀን እስኪመስል የተደረገው ቅስቀሳ በዕለቱ የሆቴል ቤት መኝታ ክፍሎችን የሚያጣብበው  እድምተኛ ጉድ ያሰኛል፡፡ አብዛኛው ፍቅረኛ በዚህ መልኩ እንደሚያሳልፍ ቀደም ያሉት ተሞክሮዎች ያሳያሉ፡፡ አንድ ወቅት ላይ ከውጭ የመጣ እንግዳ ለማሳረፍ ፈልገው መኝታ ያጣ አንድ እንግዳ ተቀባይ ተቋም አስታውሳለሁ፡፡ በአሁኑም ይቀየራል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ዛሬ ኤች አይ ቪ ኤድስ እንደገና በተንሰራራበት ጊዜ እና ሁሉም ጥንቃቄ እንዲያደርግ በሚመከርበት ጊዜ መዘናጋት እንዳይፈጠር መጠንቀቁ ይበጃል፡፡

Published in መዝናኛ
Friday, 10 February 2017 18:12

ሙዚቃና ሙዚቀኞቻችን

ሙዚቃና ሙዚቀኞቻችንሙዚቃ አእምሮን ኮርኩራ የማሳዘን ወይም የማስደሰት ኃይል ያላት መድረክ ነች ሙዚቀኞችም የአድማጭን አእምሮ በትዝታ ተመስጦ እንዲተክዝ በደስታ ተሞልቶ እንዲዝናና በድምፃቸውና ስሜትን በሚነካ ግጥማቸው ያለፈውን እንዲያስታውስ የወደፊቱን እንዲተልም የሚያደርጉ የሰው ልጅ የቅርብ ጓደኞች ናቸው::

በአገራችን የሙዚቀኞቻችን ሙያ ትላንትና ሲናቅና እንደ ተራ ነገር ሲቆጠር የቆየ ቢሆንም ዛሬ ሙያውና ሙያተኞቹ ሊወደዱና ሊደነቁ ከተቻለበት ደረጃ ላይ ተደረሷል፡፡ ይህም ለፈጠራ መዳበር ትልቅ መድረክ ሊሆን በቅቶአል ይህ በዚህ እንዳለ ከሙዚቀኞቻችን የሚታዩ አንዳንድ ድክመቶች በአፋጣኝ ቢታረሙ የአድማጮቻቸውን ቀልብ በመሳብ ተወዳጅነታቸው የጠነከረ ይሆናል እውቀታቸውም ይደረጃል ሙያውም ጥልቀትና ስፋት እያገኘ ይሄዳል::

 አድማጭ ዘፈኖች ሲደጋገምበት አንደኛው ድምፃዊ  የተጫወተውን ሌላው ቀየር አርጎ ሲጫወተው (ጋራዥ) እና የመሳሰሉት ስሞች በመስጠት ጨርሶ ሊተወው ከማይችለው ሙዚቃ ጋር አብሮ ሲራመድ ቆይቷል አሁንም እየተቀየረ አይደለም ኢትዮጵውያን ቋንቋችን ሰፊ ባህላችን ብዙ እንደመሆኑ መጠን ግጥሞች ሁልጊዜ አዲስ ለመሆን የሚያግዳቸው ነገር አይኖርም ትጋቱና ፈጠራው ሳያሰልስ ጥቅም ላይ እንዲውል ከተደረገ ይህን በሚመለከት ረገድ የቋንቋ ድህነት የለብንምና ሙዚቀኞቻችን የራሳቸው  ግጥም ሆነ ሌላው የሚገጥምላቸውን በተቻለ መጠን ትኩስ እያደረጉ ቢያቀርቡት አድማጭ ለሙዚቀኞቹ ያለው ፍቅርም ሁልጊዜ አዲስ ይሆናል::  

    

                           (የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ቅዳሜ መስከረም 20 ቀን 1976 ዓ.ም)

Published in መዝናኛ
Friday, 10 February 2017 18:08

ውል እና አስገዳጅነቱ

አመልካች፡- ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ

ተጠሪዎች፡-1/ አቶ በለጠ ማንደፍሮ (ስሙ የተቀየረ)

2/ ወ/ሮ ካሰች ባይሰጠኝ (ስሟ የተቀየረ)

   ጉዳዩ ለትምህርት (ለስልጠና) የተደረገ ወጪ በውሉ መሠረት ይመለስልኝ በማለት አመልካች የመሠረተው ክስ ነው፡፡ ከመዝገቡ እንደሚታየው 1ኛ. ተጠሪ በውሃ ኢንጂነሪንግ የማስትሬት ዲግሪ ትምህርቱን በአመልካች ድጋፍ እና ትብብር ፈቃድ ወደ ቤልጂየም አገር ሄዶ እንዲማርና ተምሮ ሲመለስም ለተማረበት ሁለት ዓመት ሦስት እጥፍ ማለትም ስድስት ዓመት አመልካችን ለማገልገል፣ ይህን ማድረግ ካልቻለ ደግሞ ለትምህርት የወጣውን እና ለቤተሰቡ የተከፈለውን ደመወዝ በጠቅላላው ብር 190,470.00  ለአመልካች እንዲከፍል ስምምነት ተደርጓል፡፡

2ኛ. ተጠሪም 1ኛ. ተጠሪ ግዴታውን ባይወጣ ባልተነጣጠለ ኃላፊነት ገንዘቡን ለመክፈል ግዴታ ገብታለች፡፡ ስለዚህም ሁለቱም ተጠሪዎች ገንዘቡን ይከፍሉ ዘንድ ይወሰንልን በማለት ነው አመልካች ክሱን የመሠረተው፡፡

ክሱ የቀረበለት የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት መደበኛ ችሎት ተጠሪዎች የሰጡን መልስ ካየ በኋላ 1ኛ. ተጠሪ በአሁኑ ጊዜ በመማር ላይ ያለ እንደሆነ ማስረጃ ቀርቦልኛል የሚል ምክንያት በመስጠት ክሱን ሰርዟል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ አመልካች የተሰጠውን ትዕዛዝ በመቃወም በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ በማቅረቡ ክርክሩ የተሰማ ሲሆን፣ በመጨረሻም ፍ/ቤቱ ይግባኝ የተባለበትን ትዕዛዝ አፅንቶታል፡፡ የሰበር አቤቱታውም የቀረበው በዚህ ላይ ነው፡፡

አመልካች በፃፈው ማመልከቻ በሥር ፍ/ቤቶች ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተፈፅሞአል የሚልበትን ምክንያት በመግለፅ ስህተቱ ይታረምለት ዘንድ ጠይቋል፡፡ ሰበር ሰሚው ፍ/ቤትም አቤቱታውን መሠረት በማድረግ ተጠሪዎችን አስቀርቦ ክርክሩ ተሰምቷል፡፡ ክርክሩ የተሰማው በሥር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ በግራ ቀኝ ወገኖች የተገባውን ውል መሠረት ያደረገ ነው ወይስ? በሚለው ጭብጥ ላይ ነው፡፡ በመሆኑም ጭብጡን ግራ ቀኝ ወገኖች ካሰሙት ክርክር አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ እና ከሕጉ ጋር ተገናዝቦ ተመርምሮአል፡፡

ግራ ቀኝ ወገኖች ካቀረቡት ክርክር መገንዘብ እንደተቻለው ለክሱ መነሻ የሆነው ውል በግራ ቀኙ መካከል ስለመደረጉ እና 1ኛ. ተጠሪም ወደቤልጅየም አገር ሄዶ የማስተርስ ዲግሪውን ስለማግኘቱ አልተካደም ወይም አከራካሪ አልሆነም፡፡

ተጠሪዎች ክሱን የተቃወሙት፡-

1ኛ/ ተጠሪ የማስተርስ ዲግሪውን ካገኘ በኋላ ወደ አሜሪካን አገር በመሄድ ከፒ.ኤች.ዲ. ዲግሪ ትምህርት በመቀጠል ላይ ስለሆነ በውሉ መሠረት ተመልሶ አመልካችን ሊያገለግል አልቻለም በሚል ገንዘቡን እንዲከፍል አይገደድም የሚል ምክንያት በመስጠት ነው፡፡ የሥር ፍ/ቤቶችም ይህንን በተጠሪዎች የቀረበውን የመከራከሪያ ነጥብ እንዳለ በመቀበል ነው ክሱን ውድቅ ያደረጉት፡፡

አመልካች  1ኛ/ ተጠሪ የቀጠለውን ትምህርት ጨረሶ ሲመለስ ክሱን ማንቀሳቀስ ይችላል በማለትም ነው ክሱን የሰረዙት፡፡ አመልካች በዚህ መልኩ የተሰጠውን ውሳኔ የተቃወመው በመሀከላችን የተደረገውን ውል እና ሕጉን መሠረት ያደረገ አይደለም በማለት ነው፡፡

ክርክሩ ሊወሰን የሚገባው በግራ ቀኝ ወገኖች የተደረገውን ውል እና አግባብነት ያለውን ሕግ መሠረት በማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም ከሁሉ በፊት የውሉን ይዘት እንደዚሁም ውሉ ለተዋዋይ ወገኖች የሰጠውን መብት እና የጣለውን ግዴታ መመርመር ተገቢ ይሆናል፡፡ በክርክሩ እንደተገለፀው አመልካች 1ኛ. ተጠሪን በማስተርስ ዲግሪ ለማስተማር ግዴታ የገባ ሲሆን፤ ተጠሪዎች ደግሞ በውሉ ለተመለከቱት ዓመታት አመልካችን ለማገልገል፤ ይህ ካልተፈፀመ ደግሞ ለትምህርቱ የወጣውን ወጪ ለአመልካች ለመተካት ግዴታ ገብተዋል፡፡

1ኛ/ ተጠሪ በውሉ መሠረት ትምህርቱን ጨርሶ የማስተርሰ ዲግሪውን ያገኘ ቢሆንም ወደ አገሩ በመመለስ ለአመልካች አገልግሎት አልሰጠም ወይም ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ይህም ማለት ውሉ በሰጠው መብት የተጠቀመ (ትምህርቱን የተማረ) ሲሆን፤ ግዴታውን ግን አልፈፀመም፡፡ የፒ.ኤች.ዲ. ዲግሪ እንዲቀጥል የሚያስችለው ተጨማሪ ስምምነትም ከአመ ልካች አላገኘም፡፡

በሕጉ አግባብ የተቋቋሙ ውሎች ባቋቋሙዋቸው ሰዎች ላይ ሕግ ስለመሆናቸው በፍትሐብሔር ሕግ ቁ 1731 በተቀመጠው ድንጋጌ ተመል ክቷል፡፡ ውለታዎች ግልፅ በሆኑ ጊዜ ግልፅ ሆኖ ከሚሰ ማው በመራቅ ወይም በመውጣት በፍ/ቤት ሊተረጎሙ እንደ ማይችሉ በፍ/ብ/ሕግ. ቁ 1733 ተደንግጓል፡፡

በተያዘው የክርክር ጉዳይ መሠረት የሆነው ውል ግልፅ ነው፡፡

1ኛ.  ተጠሪ ተመልሶ አመልካችን ለማገልገል ግዴታ የገባው የማስተርስ ዲግሪውን ካገኘ በኋላ ነው፡፡ በዚህ መሠረትም ትምርቱን ጨርሶ ዲግሪውን እንዳገኘ ተረጋግ ጧል፡፡ በመሆኑም የማገልገል ግዴታውን መወጣት የሚችለው በኋላ የጀመረውን የፒ.ኤች.ዲ. ዲግሪ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ነው ለማለት የሚቻልበት የውልም ሆነ የሕግ አግባብ የለም፡፡ የሥር ፍ/ቤቶች ወደሌላኛው ጫፍ (ትምህርቱን ጨርሶ ከተመለሰ በኋላ ክሱ ይቀጥል ወደሚለው) የሄዱት ግልፅ የሆነውን ውል ግልፅ ሆኖ ከሚታየው በመውጣት እንደሆነ ነው መገንዘብ የተቻለው፡፡ ከዚህ የተነሳም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ በሕጉ አተረጓጐም ረገድ መሠረታዊ ስህተት ያለበት ነው ለማለት ተችሏል፡፡ በዚህ መሠረትም የሚከተለው ተወስኗል፡፡

 

በአያሌው ንጉሤ

Published in ፖለቲካ

የኢትዮጵያ ህዳሴ በኢንዱስትሪ ልማት እቅድ ውስጥ ወሳኝ ቦታ የተሰጠው ለአነስተኛና ጥቃቅን ተቋሞች ነው፡፡ ይህ የሆነው በከተሞች የሥራ ዕድል የሚፈጥረው ዋናው ዘርፍ ይኸው በመሆኑና የኢኮኖሚ ልማት እቅድ አንድ መሰረታዊ አላማ የሥራ ዕድል መፍጠር በመሆኑ ነው፡፡ በአነስተኛና ጥቃቅን መደራጀት የጀመሩት ብዙዎቹ ተቋሞች በሂደት የመክሰም ወይም አነስተኛና ጥቃቅን ሆነው የመዝለቅ እድላቸው ሰፊ ከመሆኑ ጋር ወደ መካከለኛና ከፍተኛ የሚሸጋገሩም አልጠፉም፡፡ ሆኖም ብዙውን ጊዜ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋሞችን የአማራጭ መጥፋት፣ የኋላቀርነት መገለጫ አድርገው የሚመለከቱ ወጣቶች በርካቶች ናቸው። በእርግጥ ተምሮ መቀጠርን እንጂ ሥራ መፍጠርን አማራጭ አለማድረግና በተቋሞቹ የሚስተዋለው የአሠራርና ቴክኖሎጂ ኋላቀርነት የድህነት እንዲሁም የኋላቀርነት መገለጫ ተደርገው እንዲወሰዱ ቢያደርግም፤ በርካቶች ይህን ተቋቁመው ውጤታማ ሲሆኑ ተስተውለዋል። በሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ተሰማርቶ ውጤታማ መሆኑን የሚገልጸው አቶ ዳኜ ፀጋዬ የህይወት ተሞክሮውን ሲያስረዳ፤ ከዓመታት በፊት ሙያ ለመልመድ በማሰብ በወር 15 ብር ብቻ እየተከፈለው ለሰባት ዓመታት ብረት ከመበየድ ጀምሮ የተለያዩ የብረታ ብረት ሥራዎችን መሥራቱንና ሙያውን በትክክል እየለመደው ሲመጣ የሚከፈለው ደመወዝም እያደገለት መምጣቱን  በሥራውም ተወዳጅነትን ማትረፉን ይናገራል።

በተቀጣሪነት እየሠራ ሳለ አንድ የተቸገረ ሰው የመበየጃ ማሽን ለመሸጥ የሚገዛው ሰው ሲያፈላልግ በመስማቱ፤ የመበየጃ ማሽኗ የምትሸጥበትን ዋጋ በማጠያየቅ በ600 ብር እንደገዛትና በሂደት ሌላ ተጨማሪ መቁረጫ ማሽን (ግራይንደር) በመግዛት ሁለቱን ማሽኖች አስቀምጦ ህይወቱን በተቀጣሪነት እየገፋ ሳለ፤ በ2005ዓ.ም የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽህፈት ቤት የእጅ ሙያ ያላቸውን ወጣቶች ለማደራጀት ጥሪ ማድረጉን ያስታውሳል። «መደራጀት ምን ይፈይድልኛል? የእጅ ሙያ ቢኖረኝ ገንዘብ የለኝ፤ አስፈላጊ ግብዓቶችስ ከየት ይመጣሉ?» በሚል ሀሳብ ጥሪውን ችላ ብሎ እንደሰነበተና ብዙዎች እየሄዱ ሲመዘገቡ ሲያስተውል ሀሳቡን በመቀየር ከነባለቤቱ በመሄድ መመዝገቡን ይናገራል።

ከአንድ ዓመት በኋላ ከተማ አስተዳደሩ የተመዘገቡ ወጣቶችን በመጥራት መሥሪያ ቦታ እንዲወስዱና በሚፈልጉት የሙያ ዘርፍ እንዲሰማሩ ሁኔታዎችን ሲያመቻች ከባለቤታቸው ጋር በመሆን አሁን እየሠሩበት ያለውንና በሻሸመኔ ከተማ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ክላስተር ግቢ ውስጥ የሚገኘውን መሥሪያ ቦታ መቀበላቸውን የሚናገሩት አቶ ዳኜ፤ በወቅቱ በ600 ብር የገዟትን አንድ መበየጃ ማሽንና አንድ መቆራረጫ(ግራይንደር) በመያዝ የድርጅቱን ስያሜ ዳኜና የሺ የብረታ ብረት ሥራ ሽርክና ማህበር በማለት ሥራቸውን 2006ዓ.ም አሀዱ በማለት እንደጀመሩ ይናገራሉ።

አቶ ዳኜ ፀጋዬ ድርጅቱ አሁን ላይ ያለበትን ሁኔታ ሲገልጽ፤ በማህበሩ የተለያዩ የብረታ ብረት ሥራዎችን የሚሠሩ 10 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፤ ሙያ ያልለመዱ ሙያውን በትክክል እስኪለምዱ ድረስ ደመወዛቸው በአንድ የበር ከ150 ብር እስከ 200 ብር እንዲሁም ሙያ የለመዱ ደግሞ አንድ በር ሰርተው 2000 ብር ድረስ ይከፈላቸዋል። ሆኖም በርካቶች ሙያ ያልለመዱ በመሆናቸው ሥራዎችን በኮንትራት በመውሰድ እንደ በሩ አይነትና መጠን በአንድ በር ከ1500 ብር እስከ 2000 ብር ድረስ ያገኛሉ። በኮንትራት የሚሠሩት ከሚወስዱት ክፍያ ባሻገር ድርጅቱ በአንድ የበር ሥራ እስከ ሦስት ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኝም ይናገራል።

«ጥቃቅንና አነስተኛ በትክክል ለተረዳው ሰው የሚለውጥ አደረጃጀት ነው። ሁልጊዜ መንግሥትን የምንጠብቅ ከሆነ ውጤት የለውም። መንግሥት አቅጣጫ ከማሳየት ባሻገር መሥሪያ ቦታ፣ አስፈላጊ ቁሳቁስና የኤሌክትሪክ አቅርቦት አሟልቷል። ለምሳሌ እኔ ይህን ሥራ ስጀምር ከተማ አስተዳደሩ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የገበያ ትስስር የፈጠረልኝ ከዚያ በኋላ በግሌ ተሯሩጬ ነው እየሠራሁ ያለው። መንግሥት የገበያ ትስስር አልፈጠረልኝም፤ ምርቴን መሸጥ አልቻልኩም በማለት አያዋጣም ብሎ መቀመጥ ትክክል ነው የሚል እምነት የለኝም። መንግሥት መስመሩን ካሳየ በዚያ መስመር ገብቶ ውጤታማ መሆን የራስን ጥረት ይጠይቃል» በማለት አቶ ዳኜ ሀሳቡን ይገልጻል።

ወጣቶች ማንኛውንም ሥራ ሳይንቁ ያለ አቅማቸውን ተጠቅመው መሥራት ከቻሉ ውጤታማ የማይሆኑበት ነገር አይኖርም። በአሁኑ ወቅት ብዙ ወጣቶች ከዩኒቨርሲቲ እና ኮሌጆች ተመርቀው የመንግሥትን ሥራ የሚጠብቁበት ሁኔታ መኖሩን የሚያስረዱት አቶ ዳኜ፤ መንግሥት ያመቻቸውን  የብድር አቅርቦት በመጠቀም ገንዘቡን ከተቀበሉ በኋላ የሚያጠፉበት አጋጣሚ መኖሩንና ይህም ውጤታማ እንዳይሆኑ እንቅፋት እየፈጠረ  ነው። ዕድገት ማሳየት የሚቻለው ወጣቶች በብድር በወሰዱት ገንዘብ መንግሥት ከሚሰጣቸው ቦታ ላይ ሆነው ሥራቸውን መሥራት ሲችሉ ብቻ ነው ባይ ናቸው።

በብረታ ብረት ዘርፍ የቤትና የግቢ በሮችን፣ መስኮቶችን እንዲሁም የተለያዩ በትዕዛዝ የሚሠሩ የብረት ውጤቶችን በመሥራት ውጤታማ እንደሆኑና ከአንድ መበየጃና መቆራረጫ ማሽን በመነሳት በአሁን ወቅት አስር መበየጃ ማሽኖች፣ አራት መቁረጫ ማሽን(ከተር)፣ ወቅታዊ ዋጋው 20 ሺህ ብር የሆነ አንድ ትልቅ መቁረጫ(ቤንች) የተባለውን ማሟላት መቻላቸውን ይገልጻሉ። በዚህም ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን ከማሟላት አኳያ አሉሚኒየም መበየጃ ማሽን ብቻ እንደሚቀራቸውና ሌሎችን ማሟላት መቻላቸውን ይናገራሉ። ሆኖም በጥሬ ገንዘብ ደረጃ ተቀማጭ ብር ባይኖራቸውም ንብረቶችን ማፍራት እንደቻሉ ያስረዳሉ። መንግሥትን በምንም ነገር አልጠብቅም በከተማዋና በተለያዩ አካባቢዎች የሚሠሩ የልማት ሥራዎችን በማየትና ከሰዎች ጋር በቀጥታ በመገናኘት እየሠራ እንደሚገኝም ነው የሚገልጸው።

አቶ ዳኜ እንደሚሉት፤ የመንግሥትን ግብር፣ የቤት ኪራይ፣ በአግባቡ የሚከፍሉ ሲሆን፤ ከዓመት በኋላ ቦታውን ለሌሎች በማስተላለፍ ወደ መካከለኛ ደረጃ ያድጋሉ። በመሆኑም በቀጣይ ሥራውን በስፋት ለመሥራት ሰፋ ያለ ቦታ ይፈልጋሉ።

በድርጅቱ ተቀጥሮ እየሠራ ያገኘሁት ወጣት ሙሐመድ ሳዶ፤ በዳኜና የሺ የብረታ ብረት ሥራ ሽርክና ማህበር ከስድስት ዓመት በፊት በወር 100 ብር ተቀጥሮ ይሠራ እንደነበርና አሁን ላይ ከዓመታት በፊት በወር ይከፈለው የነበረውን ደመወዝ በቀን እየተከፈለው እንደሚሠራ ያስረዳል። ሥራ አጥቶ መንገድ ላይ ይውል በነበረበት ወቅት እገዛ አድርግልኝ ብሎ ምንም ሙያ ሳይችል ወደ ድርጅቱ መግባቱንና ከገባ በኋላ ሙያ መልመዱንም ይገልጻል። አሁን ላይ የተለያዩ ብረታ ብረቶችን መበየድ፣ ቅርጽ(ዲዛይን) ማውጣትና ማንኛውንም በርና መስኮት መሥራት መቻሉን ገልጾ፤ ወደፊት በግሉ ለመሥራት ገንዘብ እያጠራቀመ እንደሚገኝ ነው የሚያስረዳው።

የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራ ፈጠራና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ዓለሙ ጎንፋ፤ በከተማዋ የሚገኙ ወጣቶች የዘርፉን ጠቀሜታ በመረዳት ወደ ሥራው እንዲገቡ እየተደረገ ሲሆን፤ በአገልግሎትና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ በርካታ ወጣቶች ከራሳቸው ባሻገር ለተወሰኑ ወጣቶችም ቢሆን የሥራ ዕድል እየፈጠሩ ይገኛሉ። ከዚህ በፊት በጥቃቅንና አነስተኛ የነበሩት ደግሞ ወደ መካከለኛ እንዲሸጋገሩም ድጋፎች አልተለዩም ባይ ናቸው።

በከተማዋ ሥራ የማማረጥ ሁኔታ መኖሩንና የተወሰነው ክፍል የዘርፉን ጠቀሜታ በመረዳት ሠርቶ እየተለወጠ ሲሆን፤ አንዳንዱ ደግሞ የዘርፉን ጠቀሜታ ካለመረዳት ጥቅም እንደሌለውና ተደራጅተው መሥራት የማይፈልጉ ወጣቶችና የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር በተያያዘም ተገቢውን ድጋፍ ባለመስጠት ምክንያት ጠቂት ሰዎች ብቻ በዘርፉ ተደራጅተው እንዲሠሩ ሆነዋል። በ2009ዓ.ም በከተማዋ ሥራ አጥ ወጣቶችን ቁጥር ለመቀነስና ለ7ሺ23 ሰዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑንና እስካሁን 3ሺ 488 ማለትም 49 ነጥብ 6 በመቶ ሥራ አጦችን መመዝገብ መቻሉን ያስረዳሉ። አነስተኛ ግምት በተሰጠው ሥራ ከፍተኛ ቦታ መድረስ ይሏል ይህ ነው፡፡

 

በዑመር እንድሪስ

Published in ኢኮኖሚ

አሌክሲ ናቫልኒ

የሩስያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዋነኛ ተቀናቃኝ የሆኑት አሌክሲ ናቫልኒ ፈፅመውታል በተባለው የገንዘብ ማጭበርበር ወንጀል በአምስት ዓመታት እስር እንዲቀጡና 8ሺ500 ዶላር እንዲከፍሉ አንድ የአገሪቱ ፍርድ ቤት ትናንት ወስኖባቸዋል፡፡ ከአገሪቱ ዋና ከተማ ሞስኮ በስተምስራቅ አቅጣጫ 800 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የኪሮቭ ከተማ የታየው የናልቫኒ ክስ ውጤቱ ግለሰቡን ከሚቀጥለው ዓመት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፉክክር ውጭ እንደሚያደርጋቸው እየተዘገበ ይገኛል፡፡ 

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንንና ፓርቲያቸውን በፅኑ የሚቃወሙት ጎልማሳው ናቫልኒ ውሳኔው የተላለፈባቸው የኪሮቭ ግዛት አስተዳዳሪ ለነበሩት ኒኪታ ቤልክ አማካሪ ሆነው ይሠሩ በነበሩበት ወቅት ከአንድ ኩባንያ 16 ሚሊዮን ሩብል (500ሺ ዶላር) አጭበርብረው ወስደዋል ተብለው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት እ.አ.አ በ2013 ተከስሰው የአምስት ዓመታት እስር ተፈርዶባቸው ነበር፡፡ ውሣኔውም ከናልቫኒ ደጋፊዎች፣ ከአሜሪካና፣ ከአውሮፓ ኅብረት ሰፊ ተቃውሞ ገጠመው፡፡

በመቀጠልም የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት (European Court of Human Rights) ናልቫኒ ፍትሃዊ ፍርድ እንዳልተሰጣቸው በመግለፅ ውሳኔው በድጋሚ እንዲታይ ጥሪ አቀረበ፡፡ የሩስያ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ባለፈው ዓመት ውሳኔው ውድቅ እንዲሆን አደረገውና ግለሰቡ ነፃ ወጡ፡፡ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤትም ውሳኔው የግለሰቡን በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን የመግለፅ መብታቸውን የነፈገ ፖለቲካዊ ሴራ በመሆኑ የሩስያ መንግሥት ለግለሰቡ 67ሺ ዶላር ካሳ እንዲከፍል ጠየቀ፡፡ ባለፈው ረቡዕ ጥፋተኛ ናቸው ያስባላቸው ውሳኔም ይኸው ነፃ ሆነው የነበሩበት ክስ ነው፡፡  

 የአምስት ዓመታት እስራትና የ8ሺ500 ዶላር ቅጣት የተበየነባቸው የ40 ዓመቱ የሕግ ባለሙያና ፖለቲከኛ አሌክሳንደር ናቫልኒ፣ ከውሳኔው በኋላ በሰጡት አስተያየት ውሳኔው ከቀጣዩ ዓመት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እርሳቸውን ለማግለል በፕሬዝዳንት ፑቲን አስተዳደር የተሸረበ ፖለቲካዊ ሴራ እንደሆነ ገልፀው፣ ይግባኝ እንደሚጠይቁና ለቀጣዩ ዓመት ፕሬዝዳንታዊ የምርጫ ፉክክር ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

“ሕገ መንግሥቱ በምርጫው እንድወዳደር ስለሚፈቅድልኝ ሕገ መንግሥታዊ መብቴን ተጠቅሜ በምርጫው እወዳደራለሁ፤ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ፈፅሞ አልቀበለውም” ያሉት ናቫልኒ፣ ውሳኔው ክሬምሊን እርሳቸውን አደገኛ/አስጊ አድርጎ ስለመቁጠሩም ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም፣ “ሩስያ የተረጋጋች፣ ከሙስና የፀዳችና ሀቀኛ አገር እንድትሆን ፍላጎት ያላቸውን የብዙኃንን ፍላጎት ወክዬ መታገሌን እቀጥላለሁ” በማለት ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል ጥፋተኛ ተብለው ነፃ የወጡበት የክስ መዝገብ ከአሁኑ ጋር ፍፁም ተመሳሳይ እንደሆነና የአሁኑ ክስና ውሳኔው ከመጀመሪያው ጋር ተመሳሳይ መሆኑ ምን ያህል ፖለቲካዊ ዓላማ እንዳለው በግልፅ እንደሚያሳይም ናቫልኒ ተናግረዋል፡፡ 

ብሪታኒያ በሚገኘው ሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት የሩስያ ጥናት ትምህርት ክፍል የጥናትና ምርምር ባለሙያ የሆኑት ኢጎር ሱትያጊን ለአልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገሩት፣ ውሳኔው የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ደካማነት ያሳያል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ደካማ የሚባሉትን ተቀናቃኞቻቸውን ስለማሸነፋቸው እርግጠኛ መሆን ስለማይችሉ እያንዳንዱን ተፎካካሪዎቻቸውን ለማጥፋት የሚያደርጉት ሴራ ማሳያ እንደሆነም ባለሙያው ገልፀዋል፡፡

ታዲያ የአሌክሲ ናቫልኒ እስራት በሚቀጥለው ዓመት ይደረጋል ተብሎ ቀጠሮ በተያዘለት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ፖለቲከኞችና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡  

“የግለሰቡ እስራት በቀጣይ ዓመት የሚካሄደውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተዓማኒነቱን አያሳጣውም ወይ” ተብለው የተጠየቁት የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ፣ “መሰል እሳቤዎች ተቀባይነት የላቸውም ብለን እናምናለን” ብለዋል፡፡

የሩስያ ሕግ ወንጀለኛ ተብሎ የተፈረደበት ማንኛውም ግለሰብ ለአስር ዓመታት ያህል ለፖለቲካ ሥልጣን መወዳደር እንደማይችል ይደነግጋል፡፡

የሕግ ባለሙያውና ፖለቲከኛው አሌክሲ አናቶሊቪች ናቫልኒ፣ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ቀልብ መሳብ የጀመሩት  እ.አ.አ ከ2009 በኋላ ነው፡፡ በሩስያ የተንሰራፋውን የሙስና ወንጀልና ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን በመቃወም የተደረጉትን የተቃውሞ ሰልፎች በመምራት ወደ ፖለቲካው ዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪነት ብቅ ማለት የጀመሩት ግለሰቡ፣ እ.አ.አ በ2013 ለሞስኮ ከተማ ከንቲባነት በምርጫ ተወዳድረው ሁለተኛ ደረጃን ማግኘታቸው ታዋቂነታቸውንና ተፅዕኖ ፈጣሪነ ታቸውን ይበልጥ ጨመረላቸው፡፡ ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል የተባለው ታዋቂ ጋዜጣ በ2012 አሌክሲ ናቫልኒን “ቭላድሚር ፑቲን አጥብቀው የሚፈሯቸው ሰው” ብሎ ሰይሟቸው ነበር፡፡   

       እንግዲህ በበርካታ ሩስያውያን ልብ ውስጥ መግባት የቻሉት የሕግና የኢኮኖሚ ምሁሩ ናቫልኒ ታዋቂነታቸውና ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው እየናረ መጥቶ በቀጣዩ ዓመት በሩስያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር አቅደው የምርጫ ዘመቻ ለማድረግ የሚያ ስችላቸውን ገንዘብ በማሰባሰብ ላይ እያሉ ነው ወንጀለኛ ተብለው ወደ ወህኒ የወረዱት፡፡

Published in ዓለም አቀፍ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።