Items filtered by date: Sunday, 12 February 2017

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለዝግጅት ክፍላችን በላኩት ደብዳቤ ቅዳሜ ጥር 27 2009ዓ.ም  ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በግቢው ውስጥ ባዘጋጁት ፕሮግራም ላይ እንድንገኝ ጋበዙን፡፡ እኛም የዩኒቨርሲቲውን ጥሪ በማክበር በተባለው ቀንና ሰዓት በዩኒቨርሲቲው ባህል ማዕከል በር ላይ ተገኘን፡፡ በተባለው ሰዓት ብንደርስም የባህል ማዕከሉ በሮች ስላልተከፈቱ በርካታ ደቂቃዎችን ጠበቅን፡፡

  ቀደም ሲል በርካታ ተዋናዮችን ያፈራው፣ ብዙዎች ቀንና ለሊታቸውን ያሳለፉበት ባተሌው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል በሩን ከርችሞ ዝምታን ቢመርጥም አንድ ድግስ እንደያዘ ግን በበሩ ቀዳዳዎች እያሾለቁ የበሩን መከፈት ከሚጠባበቁ የቴአትር አፍቃሪያን ችኮላ መረዳት ይቻላል፡፡ 

     ከትራጄዲ እስከ ኮሜዲ፣ ከባህል ቴአትር እስከ ዘመናዊ ቴአትር፣ ከልማታዊ ቴአትር እስከ አዝናኝ ቴአትር ለረጅም ዓመት ሲመደረክበት የቆየው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ባህል ማዕከል ለዛሬም አንድ ለየት ያለ ድግስ እንዳሰናዳ ለመገመት አልተቸ ገርንም፡፡ የቴአትር ቤቱን ስራዎች የሚከታተሉ በርካታ ተመልካቾች የበሩን መከፈት እየተጠባበቁ ቢቆዩም ከምሸቱ አንድ ሰዓት ነው በሩ የተከፈተው፡፡

   የአዳራሹ በር ሲከፈት ግን ለመግባት የሚያጓጓ አልነበረም፡፡ ሌላ ጊዜ በሚቀርቡ ቴአትሮች ላይ ብዙዎች ተጋፍተው ጉልበት ያለው ቅድሚያውን ይዞ በተመቻቸ ቦታ ቴአትሩን ተመልክቶ መውጣት የተለመደ ነበር፡፡ ቅዳሜ ጥር 27ቀን 2009ዓ.ም ግን በተቃራኒው መድረኩ እና አዳራሹ በጨለማ ተውጦ ጨለማውን ለመስበር የሚዳክሩ በርካታ ሻማዎች ብቻ እዛና እዛ ይታያሉ፡፡ ሻማ ማብራት ከደስታም ከሀዘንም ጋር ቢያያዝም የማዕከሉ ሻማ ግን ሀዘንን ለመግለጽ እንደበራ ለማወቅ በአዳራሹ ዙሪያ ከተሰለፉ ተዋናዮች የፊት ገጽታ መረዳት ይቻላል፡፡

    ጨለማውን እና ሀዘን የዋጠውን የአዳራሽ ክፍል ደፍሮ ገብቶ ወንበር አግኝቶ የተቀመጠ ሰው ፊቱን ወደ ላይ እና ወደ ጣራው ካማተረ «ይመችሽ፣ ምን ሆነሃል?፣ ማን ፉል አለ!፣ ተይ እንጂ፣ ለሁላችን፣ በል ተወኝ፣ እንደልብ ነኝ...» እና መሰል ቃላት በነጭ ወረቀት ተጽፈው በግድግዳው ላይ ተለጥፈው ይመለከታል፡፡ እነዚህ ቃላት በደመነፍስ እና በግዴለሸኝነት የተለጠፉ የግድግዳ ማስዋቢያዎች እንዳልሆኑ ገምተናል፡፡  ግምታችንን ለማረጋገጥ ስንጠይቅ እና ሙዚቃዊ ቴአትሩ መቅረብ ሲጀምር የግድግዳ ላይ ፅሁፎቹ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤትን በመምህርነት ለረጅም ዓመት ያገለገለው እና የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር አባት መራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያ በህይወት እያለ የሚናገራቸው የርሱ ብቻ መገለጫዎች መሆናቸውን ተነገረን፡፡ የባህል ማዕከልን አዳራሽ በዚህ መልኩ ከገለጽኩ እስኪ ቴአትሩ ስለተዘጋጀለት አንጋፋው አባተ መኩሪያ ትንሽ ላስተዋውቅ፡፡ 

       ህዳር 10ቀን1932ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ አዋሬ አካባቢ ከአባቱ አቶ ስለሺ ማንደፍሮ እና ከእናቱ ወይዘሮ ውብነሽ መኩሪያ የተወለደው መራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያ አያቱ ልጅ ስላልነበራቸው ወስደው ስላሳደጉት በእርሳቸው ስም እየተጠራ ማደጉን በአንድ ወቅት በተደረገለት ቃለ ምልልስ ተናግሯል፡፡ ጭንቀትን እና ብስጭትን አጥብቆ የሚጠላው የቴአትር አዘጋጁ አባተ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት መማሩን የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት መምህሩ አቶ ጳውሎስ አእምሮ ባሳተሙት የመራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያ የህይወት ታሪክ መጽሄት ላይ አትተዋል፡፡

  አያቱ ነገረ ፈጅ እንዲሆን ቢፈልጉም ጥበብ የጠራችው መራሂ ተውኔት አባተ ከኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ጀምሮ ሙዚቃን ማዘውተር ጀመረ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ኮሌጅ ሲገባም በስነ ጽሁፍ ስራቸው ስኬታማ ከነበሩት ከዶክተር ዮናስ አድማሱ እና ከዶክተር ፊሊፕ ካፕላን ጋር መገናኘቱ ይበልጥ ወደ ቴአትሩ እንዲቀርብ በር ከፈተለት፡፡ ከዶክተር ፊሊፕ ጋር በረዳት አዘጋጅነት የተውኔት ዝግጅት ሙያን የጀመረው አባተ ከ40 ዓመት በላይ ባስቆጠረው የቴአትር ህይወቱ ላይ በርካታ ቴአትሮችን አዘጋጅቶ ለመድረክ አብቅቷል፡፡

    በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የቀድሞው ኪነ ጥበብ ወቲአትር የአሁኑ ባህል ማዕከል ሲቋቋም አባተ የመጀመሪያው ተቀጣሪ ሆነ፡፡ በማዕከሉ ውስጥ የእነ መንግስቱ ለማ፣ ጸጋዬ ገብረ መድህን፣ ገብረክርስቶስ ደስታ እና ዮሐንስ አድማሱ  ግጥሞች ሲቀርቡ ከመድረኩ ፊት ለፊት እንደማይጠፋ በርሱ የሕይወት ታሪክ ላይ ጥናት ያደረገው መምህር ጳውሎስ አእምሮ ይገልፃል፡፡ ወደ ስራ ህይወቱ ስንገባ መራሂ ተውኔት አባተ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በዳይሬክተርነትም ሰርቷል፡፡ የተለያዩ ቴአትር ቤቶችንም በአስተዳዳሪነት እና በአዘጋጅነት አገልግሏል፡፡

   የቴአትር አዘጋጁ አባተ መኩሪያ አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ተዟዙሮ ቴአትርን አጥንቷል፡፡ በማዘጋጃ ቴአትር ቤት፣ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት እና በብሄራዊ ቴአትር ቤትም በቴአትር አዘጋጅነት ለበርካታ ዓመታት ሰርቷል፡፡ አባተ ከዚህ በተጨማሪ ረጅሙን ሕይወቱን ያሳለፈበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤትም በርካታ የቴአትር ባለሙያዎችን እንዲያፈራ ያደረገ ከፍተኛ የቴአትር ባለሙያ መሆኑን የተጻፈው የህይወት ታሪኩ ያስረዳል፡፡

   መራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያ በአውሮፓ እና በአሜሪካ የተለያዩ ሀገራት ተዟዙሮ ኦፔራን፣ ሚዲያና ኮሙኒኬሽንን፣ የቴአትር አዘገጃጀትን እና አተዋወንን በአጠቃላይ ስለ ቴአትር በርካታ የሙያ ማሻሻያ ስልጠናዎችን ወስዷል፡፡ አባተ ቀደም ሲል በተለያዩ መድረኮች ላይ አዘጋጅቶ ለእይታ ካበቃቸው ቴአትሮች ውስጥ መልክዓ ምድር፣ ሀሁ በስድስት ወር፣ መልክዓ ወዛደር፣ የመንታ እናት፣ መቅደም፣ ጋሞ፣ ኦቴሎ፣ ቴዎድሮስ፣ አሉላ አባነጋ፣ ያላቻ ጋብቻ፣ ሊስትሮ ኦፔራ፣ ኤድፒስ ንጉስ፣ አፋጀሽኝ ከቀድሞዎቹ ተጠቃሽ ስራዎቹ ናቸው፡፡ ከቅርብ ስራዎቹ ደግሞ ከአራት ዓመት በፊት ለብሄሮች ብሄረሰቦች ህዝቦች በዓል ማድመቂያ በሚል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር በጥምረት ያዘጋጀው«ሀገር ማለት ሰው ነው» እና ሌሎችም ተጠቃሽ ስራዎቹ ናቸው፡፡

        ከበርካታ ስኬታማ የቴአትር ባለሙያዎች ጀርባ ስሙ የማይጠፋው መራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያ ሀምሌ 13 ቀን 2008ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ሲሰማ ግን የሙያ አጋሮቹ፣ ተማሪዎቹ እና የቴአትር አፍቃሪያን ልብ ተሰበረ፡፡

   በርካታ ተተኪ መምህራን እና የቴአትር ባለሙያዎችን ያፈራው መራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያ በተለይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት ውስጥ ስሙ በጉልህ ይነሳል፡፡ቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤትም በቴአትር አባቱ አባተ ሞት ቢያዝንም ስራዎቹን ህያው ለማድረግ ደፋ ቀና እያለ ይገኛል፡፡ 

    የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ‹‹ቴአትር ኢን መልቲሚዲያ›› ለሚለው ስልጠና (ኮርስ) ማሟያ ለተመራቂ ተማሪዎች አንድ የቤት ስራ ይሰጣል፡፡ ይኸውም ለኮርሱ ማሟያ አንድ ሙዚቃዊ ቴአትር እንዲያዘጋጁና ለመድረክ እንዲያበቁ ነበር፡፡ የቤት ስራውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል አንዱ እና በብዙ ስራዎቹ መራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያን ይወክላል ተብሎ ግምት ያገኘው አቶ ቻላቸው ፈረጅ ስራውን ከአባተ መኩሪያ ጋር ሊያይዘው ወሰነ፡፡

    የትምህርት ቤቱ መምህር እና « እኔን የሰራኝ ጋሽ አባተ ነው» በሚል ንግግሩ የሚታወቀው ተመራቂው አቶ ቻላቸው ፈረጅ ለአንጋፋው የእውቀት አባቱ መራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያ መታሰቢያ እንዲሆን «ትዝታ ዘ አባተ» በሚል ርዕስ መቦጫጨር ጀመረ፡፡ ቻላቸው ከክፍል አጋሮቹ ጋር በመሆንም ሀሳቡን አዳብሮ ወደ መድረክ አበቃው፡፡ የዝግጅቱን የመጨረሻ ስራም ቅዳሜ ጥር 27 ቀን 2009ዓ.ም አቅርቧል፡፡ 

   በአቶ ቻላቸው ፈረጅ ተጽፎ እና ተዘጋጅቶ ለእይታ የበቃው ትዝታ ዘ አባተ ሙዚቃዊ ተውኔት ላይ ከ30 የማያንሱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ ሁለት ሰዓት በወሰደው በዚህ ሙዚቃዊ ተውኔት ላይ አርቲስት ተስፋለም ታምራትን ጨምሮ ሌሎች በዩኒቨርሲቲው እየተማሩ የሚገኙ በርካታ ተዋናዮች ተሳትፈዋል፡፡

     ቴአትሩ ከስክሪፕት ባሻገር በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህራን እና ተማሪዎችም የተቀናበረ ሙዚቃዊ ይዘትም ነበረው፡፡ መራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያ በተደጋጋሚ የሚናገራቸውን ቃላቶች ተዋንያን ሲጠሩ በሙዚቃ መሳሪያ ታጅበው ነው፡፡ ለምሳሌ «ይመችሽ» የሚለውን የአባተን ቃል አንድ ተዋናይ ሲናገረው ከይመችሽ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል ሙዚቃም በተጓዳኝ ይለቀቃል፡፡

     በተውኔቱ ሌላው ገጽታ ላይ ስለ ጋሽ አባተ አስተያየታቸውን ከሰጡ የሙያ ልጆቹ ውስጥ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ፣ አርቲስት አበበ ባልቻ፣ አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም፣ አርቲስት ኩራባቸው ደነቀ፣ መምህር ተስፋዬ እሸቱ እና ሌሎች የሙያ አጋሮቹን አስተያየት የሚመለከት ምስልም በመድረኩ አናት ላይ ይታያል፡፡

     መራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያ የኢትዮጵያ ሙዚቃዊ ቴአትር እድገት ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ባለሙያ ነው፡፡ ለዚህም ነው እርሱን የሚዘክረው ቴአትር በሙዚቃዊ ስልት እንዲቀርብ የተደረገው፡፡ በቴአትሩ ላይ ሁሉም ተዋንያን በየተራ እየተነሱ መራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያ የሚጠቀማቸውን ንግግሮች በሙዚቃዊ መሳሪያ ታግዘው ይናገራሉ፡፡

 በተውኔቱ ላይ ከ30 በላይ የሚሆኑ ተዋንያን ተሳትፈዋል፡፡ ተዋንያኑ በሁለት ተከፍለው በአንድ ምድብ ወንዶች በሌላ ምድብ ሴቶች ተቧድነው የፍቅር አጀማመርን በአባተ መኩሪያ ቃላቶች ሲመሰርቱም ታይቷል፡፡ አንድ ሴት ከወንድ ልጅ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ስትተዋወቅ የምታሳያቸውን ምልክቶች እና የአነጋገር ስልትም በአባተ መኩሪያ አገላለጽ ክርክር ሲያካሂዱ ለተመልካች አሳይተዋል፡፡

    የሙዚቃዊ ተውኔቱ ጡዘት ከሮ እየሄደ በመጨረሻ ከድራማው ሀዘን ድባብ ለመውጣት ሁለቱን ጓደኛሞች በማጋባት በደስታ እና በጭፈራ ተውኔቱ እንዲያልቅ ተደርጓል፡፡ ቴአትሩ ምንም እንኳ በርካታ ሀሳቦች ቢኖሩትም ሁሉም ሃሳቦች ግን የሚያጠነጥኑት በመራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያ ስራ፣ ህይወት እና አነጋገር ላይ መሆኑን በመካከል በሚሰነዘሩ ቃላት መረዳት ይቻላል፡፡

ጋሽ አባተ ታላቅ ነህ

መቼም አንረሳህም»

  በሚል ዜማ በቀረበው በዚህ ሙዚቃዊ ተውኔት ላይ የመራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያ ባለቤት ወይዘሮ ምህረት ባረጋን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ቴአትር ተመልካቾች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ጥበባት ኮሌጅ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬን ጨምሮ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተወጣጡ ጋዜጠኞችም ታድመዋል፡፡

   የተውኔቱ ደራሲ እና አዘጋጅ አቶ ቻላቸው ፈርጅ መራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያን በቃላት መግለጽ ከባድ መሆኑን ይናገራል፡፡ ይሁን እንጂ አባተን በአጭሩ ለመግለጽ ያህል «ጋሽ አባተ ማለት በኢትዮጵያ የዘመናዊ ቴአትር ታሪክ ውስጥ ዋና ተዋናይ እና የቴአትር ባለውለታ ነው፡፡ ከ100 ዓመት በላይ ባስቆጠረው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር ውስጥ መገለጫ ከሆኑት ባለሙያዎች ውስጥ አባተ የመጀመሪያው ነው፡፡ ጋሽ አባተ በአጭሩ ራሱን የቻለ ተቋም ነው፡፡ ይህንን ተቋም የሆነ ባለሙያ ማጣት ለቴአትር ከባድ ሀዘን ነው» ሲል ገልጾታል፡፡

   ቴአትሩን ያዘጋጁት በዋናነት በሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ለሚወስዱት ኮርስ ማሟያ ቢሆንም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሙያ አባታቸውን የማስታወስ እድል ማግኘታቸው እንዳስደሰተው የተናገረው ደራሲና አዘጋጅ ቻላቸው፣ ቴአትር ከመዝናናት እና ከማስተማር ባለፈ የቀድሞ ባለውለታዎችንም የመዘከር እድል የሚፈጥር ትልቁ የመግባቢያ መሳሪያ እንደሆነም ነው የጠቆመው፡፡

   እየወሰዱ ያሉት ስልጠና ሰፊ ነጻነት የሚያላብስ መሆኑ መራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያን ለመዘከር እድል እንደሰጣቸው የተናገረው ቻላቸው፣ አባተ በሕይወት ዘመኑ በርካታ ትዝታዎች እና የርሱ ብቻ የሆኑ ቃላት እንዳሉት፣ እነዚህን ቃላት በተቻላቸው መጠን በቴአትሩ ውስጥ ለመጠቀም መሞከራቸውን ገልጿል፡፡  ቴአትሩን ከመጻፍ ጀምሮ እስከ ማዘጋጀት ድረስ 20 ቀናት ብቻ እንደወሰደባቸው የገለጸው ደራሲና አዘጋጅ ቻላቸው ፈረጅ፣ ትዝታ ዘ አባተ ሙዚቃዊ ቴአትር በባህል ማዕከል ብቻ ሳይገደብ በብሄራዊ ቴአትር ቤትም የሚቀርብበትን እድል ለማመቻቸት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

    « እውነት ለመናገር ይህን ያህል ጥሩ ስራም ይሆናል ብዬ አላሰብኩም፡፡ ጥቂት ተመልካቾች ጠርተን ብዙ መምጣቱ ቢያስገርመኝም የመጣው ተመልካች ሲያጨበጭብ ስትመለከት ደግሞ አሪፍ ስራ እንዳቀረብክ ይሰማሃል፡፡ እኔ ግን አሁንም አልረካሁም፡፡ በቀጣይ ከዚህ በተሻለ ለመስራት እንደ አበበ ባልቻ እና ፍቃዱ ተክለማርያም ከመሳሰሉ የሙያ ልጆቹ እና ከቤተሰቦቹ ጋር ተነጋግረን አሪፍ ስራ ለመስራት አስበናል»ያለው የቴአትሩ ደራሲና አዘጋጅ ቻላቸው ፈረጅ በተለይ ደግሞ የአንደኛ ዓመት ሙት ዓመቱን በተለያዩ ፕሮግራሞች ለማቅረብ ከወዲሁ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ሳይገልጽ አላለፈም፡፡

   በሙዚቃዊ ቴአትሩ ላይ በተራኪነት የተሳተፈው አርቲስት ተስፋለም ታምራት በበኩሉ ከመራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያ ጋር አብሮ የመስራት እድል ባለማግኘቱ ቁጭት እንደፈጠረበት ገልጾ፣ ወደ ዩኒቨርሲቲው ከመጣ  በኋላ ግን አባተ እና ቴአትር ያላቸውን ቁርኝት በቀላሉ መረዳት እንደቻለ ነው የተናገረው፡፡«ዩኒቨርሲቲ ማለት  እውቀትህን የምታዳብርበት ነው፡፡በተለይ ደግሞ እንደ ጋሽ አባተ የመሰሉ ጠንካራ እና ብቁ ባለሙያዎች ካሉ ታንጸህ ነው የምትወጣው» ያለው አርቲስት ተስፋለም ተውኔቱን ያዘጋጁት ለኮርስ ማሟያነት ቢሆንም በተጓዳኝ መራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያን የዘከሩበት መንገድ እንዳስደሰተው ተናግሯል፡፡

    «የጋሽ አባተ ሀሳብ እና ንግግር እኔን ጨምሮ በሁሉም ሰው ውስጥ አለ፡፡ በቴአትሩ ውስጥም ሁሉም ተዋናዮች የጋሽ አባተን ሀሳብ እና ንግግሮች ማቀንቀን እና ማስታወቅ ላይ ነው የሰራነው» ያለው አርቲስት ተስፋለም ተውኔቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተዘጋጅቶ መቅረቡ መልካም ቢሆንም ከዚህ በተሻለ ማቅረብ ግን በቀጣይ የሚወስዱት የቤት ስራ እንደሆነም ተናግሯል፡፡

   በቴአትር ብቻ ሳይሆን በየዘርፉ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆኑ ባለሙያዎች ቢፈሩም ስራቸው ተደብቆ ትኩረት አጥተው ማለፋቸው የተለመደ መሆኑን የተናገረው አርቲስት ተስፋለም፣ የመራሂ ተውኔት አባተን ስራዎች በመድረክ ማቅረብ በአንድ በኩል ስራዎቹ እንዲተዋወቁ እድል ሲፈጥር በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች ባለሙያዎችንም እንደሚያነሳሳ ገልጿል፡፡

  «በእንደዚህ ዓይነት ታሪካዊ ስራ ላይ መሳተፍ እድለኝነትን ይጠይቃል» ያለው አርቲስት ተስፋለም በቀጣይ የቴአትር ባለውለታው አባተ መኩሪያን በሚዘክሩ ቴአትሮች ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለውም ገልጿል፡፡የቀድሞ ስመ ጥር ሰዎችን በእንደዚህ ዓይነት መዘከር ፍጹም ሊበረታታ እንደሚገባ የተናገረው አርቲስቱ፣ቴአትሩ በቂ ዝግጅት ተደርጎበት በብሄራዊ ቴአትር የሚቀርብበት መንገድ እንዲመቻችም ጥሪ አቅርቧል፡፡ 

     በቴአትሩ ላይ ከተሳተፉ ተዋንያን መካከል አንዷ የሆነችው ሳምራዊት ከበደ የሁለተኛ ዓመት የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት ተማሪ መሆኗን ገልጻ፣ እንደ ተስፋለም ሁሉ በጋሽ አባተ የመማር እድል ባታገኝም በምትማራቸው በርካታ የትምህርት ዓይነቶች ላይ አባተን እና ስራውን እንደምታውቅ ሳትገልጽ አላለፈችም፡፡ የመራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ለቴአትር ትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ ቴአትር ከባድ ሀዘን መሆኑን የጠቆመችው ሳምራዊት፣ ይህን ትልቅ ባለሙያ ለመዘከር ለእርሱ ባይመጥንም የአቅማቸውን ለፍተው «ትዝታ ዘ አባተ» ሙዚቃዊ ቴአትርን ማቅረባቸው እንዳስደሰታት ተናግራለች፡፡

   «ጋሽ አባተ በህይወት እያለ በርካታ ፕሮግራሞች ተሰርተውለታል፡፡ ብዙ ስራዎቹ እውቅና አግኝተዋል፡፡ይህ ደግሞ ለቤተሰቡም ሆነ ለተተኪ ባለሙያዎች መነሳሳት ይፈጥራል» ያለችው ተዋናይ ሳምራዊት፣መራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያ በህይወት እያለ ከሚናገራቸው እና ከሰራቸው ስራዎች ውስጥ የተወሰኑት ተመርጠው በመድረኩ ላይ መቅረባቸው እንዳስደሰታት ተናግራለች፡፡ 

   በባህል ማዕከል ተገኝተው የባለቤታቸውን ስራዎች የሚዘክረውን ቴአትር የተመለከቱት ወይዘሮ ምህረት ባረጋ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለባለቤታቸው ያደረገው የማስታወስ ስራ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ አባተ በህይወት ባይኖርም ስራው ህያው መሆኑን ለመረዳት መቻላቸውን አስታውቀዋል፡፡ መራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያ አብዛኛውን ህይወቱን ባሳለፈበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በርካታ የቴአትር ባለሙያዎችን ማፍራቱን የገለጹት ወይዘሮ ምህረት፣ የሙያ ልጆቹ አባታቸውን ለመዘከር በሚያደርጉት ጥረት ሁሉ ምስጋናቸው የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

    « ለእኔ መኖር ማለት  ቴአትር መስራት ነው፡፡ እኔ በጭራሽ ሞት አልፈራም፡፡ ምክንያቱም የምችለውን ሰርቻለሁ፡፡ ብዙ ባለሙያዎችን አፍርቻለሁ» በሚሉት ንግግሮቹ የሚታወሰው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር አባት መራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ ሰባት ወር ሊሞላው ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመራሂ ተውኔት አባተ መኩሪያን ስራዎች በተለያዩ መድረኮች የማቅረብ ውጥን እንዳለውም ለማወቅ ችለናል፡፡

 

ታምራት አበራ

Published in መዝናኛ

የእንግሊዙ አርሰናል እግር ኳስ ክለብ ከዳሽን ቢራ ጋር ባለው አብሮ የመስራት ስምምነት ተተኪ ተጫዋቾችን በማፍራት ላይ ለሚገኙ 32 አሰልጣኞች የሁለት ቀን ስልጠና ሰጠ፡፡ በአዲስ አበባ ንግድ ባንክ ሜዳ  ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ አሰልጣኞች በተሰጠው ስልጠና ላይ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች አሰግድ ተስፋዬን ጨምሮ በርካታ ባለሙያዎች ተካፍለዋል፡፡

    በአርሰናል አካዳሚ ውስጥ እየሰሩ የሚገኙት ሲሞን ማክማነስ እና ካርላን ኤድጋር የካቲት 2 እና የካቲት 3 2009ዓ.ም በተሰጠው ሶስተኛ ዙር ስልጠና ላይ በአሰልጣኝነት ተሳትፈዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ የተሰጣቸውን ስልጠና በትጋት መከታተላቸውን አሰልጣኞች በተለይ ለአዲስ ዘመን ተናግረዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስልጠና ሲሰጡ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የተናገሩት አሰልጣኞቹ ኢትዮጵያ እንደዚህ ዓይነት ስልጠናዎችን አጠናክራ ከቀጠለች ውጤታማ ተጫዋች የማፍራት አቅም እንዳላትም ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

   በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ 160 ታዳጊዎችን ሰብስቦ በአስር አሰልጣኞች ስልጠና መስጠት ከጀመረ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንና የቡና ኮከብ አሰግድ ተስፋዬ በስልጠናው ላይ መሳተፉ እንዳስደሰተው ተናግሯል፡፡ የሚያሰለጥናቸውን ታዳጊዎች ስዊድንን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ውድድሮች ላይ እንደሚያሳትፍ የገለጸው አሰግድ፣ በዓለማችን ከሚገኙ ትልቅ ክለቦች ተርታ ከሚመደበው አርሰናል ክለብ በመጡ አሰልጣኞች ስልጠና መውሰድን የመሰለ እድል ላመቻቸላቸው ዳሽን ቢራ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

  «የወሰድነው ስልጠና በዓለም ላይ ተዕጽኖ ከፈጠሩ ክለቦች አንዱ በሆነው አርሰናል አሰልጣኞች መሆኑ በራሱ ተጠቃሚ ያደርገናል፡፡ እነርሱ በዋነኝነት የአሰለጣጠን ስልትን ነው ያስተማሩን፡፡ ከነርሱ በወሰድነው ስልጠና ላይ የራሳችንን እውቀት ጨምረን የተሻለ ውጤት እንደምናስመዘግብ እተማመናለሁ፡፡» ያለው  አሰግድ  አሰልጣኞቹ የህጻናት አሰለጣጠን አቅጣጫውን በአግባቡ እንዳሳዩዋቸውም ጠቁሟል፡፡

   የወሰዱትን ስልጠና ውጤት ለማየት ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ የገለጸው አሰግድ፣ በቀጣይ እንደዚህ ዓይነት ስልጠናዎችን በብዛት እና በጥራት ለመስጠት ዳሽን ቢራ ጥረቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልንም አሳስቧል፡፡ የተሰጠውን ስልጠና በልጆቹ ላይ ለመተግበር የህጻናት አሰለጣጠን ስልትን በቀላሉ መገንዘብ መቻሉን አሰግድ በተለይ ለአዲስ ዘመን ገልጿል፡፡

  አምሳሉ እስመለዓለም ሌላው ከባህርዳር መጥቶ በስልጠናው ላይ የተሳተፈ የታዳጊዎች አሰልጣኝ ነው፡፡ ከ17 ዓመት በታች በርካታ ተተኪ እግር ኳስ ተጫዋቾችን እያፈራ መሆኑን የተናገረው አምሳሉ፣ ቀደም ሲል በሌሎች የአርሰናል አሰልጣኞች ተመሳሳይ ስልጠና መውሰዱን ይናገራል፡፡ ከውጤታማው እና ከተወዳጁ አርሰናል ክለብ በመጡ አሰልጣኞች ሰልጥኖ ወደ ባህርዳር ሲመለስ ተግባራዊ ለማድረግ ተነሳሺነት እንደፈጠረበትም ጠቁሟል፡፡

   «ሁለቱንም ቀን በዋናነት የወሰድነው መሰረታዊ የአሰለጣጠን ስልቶችን ነው፡፡ በጥልቀት እና በስፋት ስልጠናውን ለመስጠት ሁለት ቀን በቂ ስላልነበር በስልቶች ላይ አተኩረው ነው ያሰለጠኑን» ያለው አሰልጣኝ አምሳሉ፣ ከእነርሱ የቀሰሟቸውን የህጻናት አሰለጣጠን ስልቶች ተግባራዊ በማድረግ የሀገሪቱን እግር ኳስ ለማሳደግ በስልጠናው ላይ የተሳተፉ ሁሉ ድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

  ዳሽን ቢራ እና አርሰናል እግር ኳስ ክለብ ለሶስት ዓመታት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የሶስት ዓመት ስምምነት ካደረጉ ሁለተኛ ዓመታቸውን አስቆጥረዋል፡፡ ዳሽን ቢራ በቀጣይ በታዳጊ ፕሮጀክት አሰልጣኝነት የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ አሰልጣኞችን እንግሊዝ ድረስ በመጋበዝ ልምድ ለማስቀሰም ከስምምነት ላይ መድረሱንም ይፋ አድርጓል፡፡

 

ታምራት አበራ

Published in ስፖርት

ኮማንደር ዓይናለም አዳነ፤

ኢትዮጵያ እና አትሌቲክስ ስፖርት በትልልቅ የውድድር መድረኮች ላይ ከተዋወቁ የወርቅ እዮቤልዩ በዓላቸውን አክብረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ከ1948ዓ.ም የሜልቦርን ኦሊምፒክ ቢጀምርም ወደ አሸናፊነት  የመጣችው ግን በ1952ዓ.ም ነው፡፡ በጣሊያን ሮም በተካሄደው ኦሊምፒክ ላይ በሻምበል አበበ ቢቂላ የማራቶን አሸናፊነት የመጀመሪያዋን የወርቅ ሜዳለያ ማጥለቋን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በሮም ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ የተጀመረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት ውጤታማነት በየጊዜው አንድ ጊዜ ከፍ ሌላ ጊዜ ዝቅ እያለ በርካታ ሜዳሊያዎች ተገኝተዋል፡፡ ቀደም ሲል ከገንዘብ ይልቅ የአገርን ስም ለማስጠራት ላባቸውን የሚያፈሱ ኢትዮጵያውያን ሯጮች በአገራቸው ህዝብ የተጣለባቸውን አደራ በአግባቡ ሲወጡ ኖረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በትልልቅ የውድድር መድረኮች ላይ ተሳትፈው ሜዳሊያ ያጠለቁ ስኬታማ አትሌቶች እንደ አሸናፊነታቸው በገንዘብ በኩል ተጠቃሚ መሆን ሳይችሉ ቀርተው ሲታመሙ ለህክምና፣ መኖሪያ ሲያጡ ለቤት መስሪያ እርዳታ ሲሰበሰብላቸው ተመልክተናል፡፡

ከአራት አሥርት ዓመታት በፊት በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ ለመሳተፍ ከወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋማት ተመርጠው ለአጭር ጊዜ ስልጠና ወስደው የሚያሸንፉ አትሌቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አገሩን ወክሎ ያለ በቂ ልምምድ እና ቁሳቁስ ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ የተሳተፈ አትሌት ከተሸነፈ ሌላ ጥያቄ እንደሚቀርብበት አስቀድሞ ያውቀዋል፡፡ የተሰጠውን ከባዱን የቤት ሥራ ሳይወጣ ቢቀር አሳማኝ ያልሆነ መረጃ ካላመጣ በስተቀር ለእስራት እና ቅጣት የተዳረጉ አትሌቶች እንደነበሩም የቀድሞ አትሌቶች ሲናገሩ ሰምተናል፡፡

በአንጻሩ ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግሥት ለአትሌቲክስ ስፖርት በሰጠው ሰፊ ትኩረት ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በተለየ በርካታ ውጤታማ አትሌቶችን በማፍራት በበርካታ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ተሳትፋ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ቀደም ሲል ኦሊምፒክን ጨምሮ በበርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ አሸንፈው የሜዳሊያ ሀብታም የገንዘብ ድሃ ሆነው ከሩጫ የተገለሉ አትሌቶች በባለሀብቶች እና የብዙ  ሚሊዮን ዶላሮች ባለቤት በሆኑ አትሌቶች ተተክተዋል፡፡

በስፖርቱ የሚገኘው የፋይናንስ ጥቅምም ይሁን ዝናው የሳባቸው በርካታ አትሌቶች በአቋራጭ ለመክበርም ይሁን ሀገራቸውን ለማስጠራት በየጫካው እና በየተራራው ላባቸውን እያፈሰሱ ልምምድ ሲያደርጉ ለመመልከት በጫካማ ቦታዎች መንቀሳቀስ በቂ ነው፡፡ ከእነዚህ አትሌቶች ውስጥ ጥቂቶቹ በሚፈጠርላቸው መልካም አጋጣሚ በክለብ ይታቀፋሉ፡፡ ጥቂቶቹ ደግሞ ክለብ አጥተው በግላቸው አሰልጣኝ ቀጥረው ልምምዳቸውን ሲያጠናክሩ እንመለከታለን፡፡

በርካታ የአትሌቲክስ ክለቦች መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ ከየክልሉ በአትሌቲክስ ስፖርት ከፍተኛ ደረጃ መድረስን ዓላማ አድርገው የሚመጡ ሯጮች ማረፊያ ናት፡፡ በከተማዋ የሚገኙ የአትሌቲክስ ክለቦች በየጊዜው ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት በሚያስቀምጡት መመዘኛ አጣርተው ያስገባሉ፡፡  

በክለብ ታቅፈውም ይሁን ሳይታቀፉ በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ ዳገታማ፣ ሜዳማና ጫካ በሚበዛባቸው ቦታዎች ጠዋት እና ማታ ሩጫን ዋና ሥራቸው አድርገው የሚሟሟቱ አትሌቶች በርክተዋል፡፡ አትሌቶቹ ህልማቸው ተሳክቶ በትልልቅ ውድድሮች ላይ ካሸነፉ አገራቸውን ማስጠራት እና ራሳቸውን በፋይናንስ ማበልጸግ እቅዳቸው ሲሆን ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ ውድድር ላይ ተሳትፈው ያመጡትን ለውጥ መመዘን ላይ አይደራደሩም፡፡

የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና እንደ ታላቁ ሩጫ በመሳሰሉ በርካታ እና ውጤታማ አትሌቶች በሚሳተፉባቸው ሩጫዎች ላይ መሳተፍ በልምምድ ላይ የሚገኙ አትሌቶች በጭራሽ ሊያልፋቸው የማይፈልጉት ዕድል ነው፡፡ አትሌቶቹ በእንደዚህ ዓይነት ውድድር ላይ መሳተፋቸው ድክመታቸውን ለማረም እና የተሻለ ዝግጅት ለማድረግ እንደሚያግ ዛቸውም አትሌቶቹ ይናገራሉ፡፡ 

በተለይ ደግሞ የረጅም ርቀት በሆነው ማራቶን ዘርፍ የሚወዳደሩ አትሌቶች በቂ የውድድር ዕድል ማጣታቸው ትልቁ ፈተና እንደሆነባቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይሰማል፡፡ በከተማ አቀፍም ይሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ በዓመት ከሁለት እና ከሦስት በላይ ውድድሮች የማይካሄዱበት የማራቶን ውድድር ለተተኪ አትሌቶች መጥፋት ምክንያት ተደርጎ ሊነሳ እንደሚችልም አትሌቶቹ ይናገራሉ፡፡

በከተማዋ ለሚገኙ አትሌቶች የውድድር ዕድል ለመፍጠር ከሞሃ ለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ ጋር ለረጅም ዓመት በጥምረት ሲሰራ የቆየው የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የውድድር ዕድሎችን በመፍጠር በኩል የሚያበረታታ ሥራ እየሰራ ይገኛል፡፡ ፌዴሬሽኑ በዓመቱ ውስጥ የክለቦች ውድድር፣ የግማሽ ማራቶን ውድድር፣ የሪሌ ውድድር፣ የማራቶን ውድድርን ጨምሮ በርካታ ውድድሮችን ያካሂዳል፡፡

ፌዴሬሽኑ ሰሞኑን ደግሞ 21ኛውን የፔፕሲ ማራቶን ውድድር በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ሰሚት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አካሂዷል፡፡ ጥር 28ቀን2009ዓ.ም በተካሄደው በዚህ የማራቶን ውድድር ላይ ከተለያዩ ክለቦች የተውጣጡ 132 አትሌቶች እና በግል የሮጡ 80 አትሌቶች በድምሩ 212 የማራቶን ሯጮች ተመዝግበው ውድድራቸውን ማካሄዳቸውን ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ፌዴሬሽኑ የውድድር ዕድል ለመፍጠር በሚል የማራቶንን ሩጫ ማዘጋጀቱ በተወዳዳሪ አትሌቶች በኩል አድናቆትን አትርፎለታል፡፡ ከሩጫው ቀን ቀደም ብሎ ተሳታፊ አትሌቶችን መዝግቦ የመሮጫ ቁጥር የሰጠው የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ለሩጫው እውን መሆን የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችንም በማከናወን መተዳደሪያ ደንቡን መሰረት አድርጎ በዘንድሮው ውድድር ላይ 212 ሯጮችን 42 ኪሎ ሜትር ከ195 ሜትር የሚሸፍነውን ውድድር እሁድ ማለዳ አስጀመረ፡፡

ይሁንና ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ ፌዴሬሽኑ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች መታወቂያቸውንና የተሰጣቸውን የምዝገባ ቁጥር እንዲያሳዩ ጠየቀ፡፡ በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ የቅድመ ምዝገባውን አጠናቀው  የተሰጣቸውን ቁጥርና መታወቂያ የያዙ እውቅና ተሰጥቷቸው ተሰለፉ፡፡ መታወቂያ ያልያዙ ነገር ግን የተሰጣቸውን ቁጥር የያዙ መሳተፍ እንደማይችሉ ቢገለጽም መረጃ ባላሟሉ አትሌቶች አሻፈረኝ ባይነት 42 ኪሎ ሜትር 195 ሜትሩን ርቀት ሮጡ፡፡ውድድሩ ሲጠናቀቅ ታደሰ አሰፋ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ቀዳሚ ሆኖ ገባ፡፡ እርሱን በመከተል ዓለማየሁ መኮንን ከኤልሚ ኤሎንዶ ሁለተኛ፣ በላቸው ዓለሙ ከፌዴራል ፖሊስ ሦስተኛ እንዲሁም አማኑኤል ተሾመ በግል አራተኛ ደረጃን ይዘው ርቀቱን ጨረሱ፡፡ ይሁን እንጂ ውድድሩን በሁለተኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ዓለማየሁ መኮንን የውድድሩን መስፈርት ባለማሟላቱ ያስመዘገበው ውጤት እንደማይያዝለት ተነገረው፡፡ ውጤቱ የተሰረዘበት አትሌት ዓለማየሁ እምባ በተሞላ ዓይኑ ምሬቱን ቢገልጽም «በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት በሩጫው ላይ ለመሳተፍ የሚያስችል መስፈርት አላሟላህም፣ ስለዚህ የሮጥከው ዋጋ የለውም» የሚል ምላሽ ተሰጠው፡፡ ፌዴሬሽኑ ከውድድሩ በኋላም አሸናፊዎችን ሲሸልም ታደሰ አሰፋን በአንደኝነት፣ በላቸው ዓለሙን በሁለተኝነት እንዲሁም አማኑኤል ተሾመን በሦስተኛነት እውቅና ሰጥቶ የገንዘብና የሜዳሊያ ሽልማት አበረከተ፡፡

በዚህ ውድድር ላይ ሁለተኛ ሆኖ ውድድሩን ካጠናቀቀው አትሌት ዓለማየሁ በተጨማሪ15ኛ ሆኖ የጨረሰው ኢሳያስ ዳታ፣26ኛ ሆኖ የጨረሰው ሳዲቅ ምስጋና፣ 28ኛ ሆኖ የጨረሰው አማረ ምንአየውም ውጤታቸው ያልተያዘላቸው አትሌቶች ናቸው፡፡
ዓመት ሙሉ ሰፊ ዝግጅት ያደረጉና በነርሱ አገላለጽ መታወቂያ ይዘው እንዲመጡ ያልተነገራቸው እነዚህ ሯጮች አቋማቸውን ለመፈተሽ ረጅሙን ርቀት ሮጠው ቢያጠናቅቁም ያሰቡት የተሳትፎ ደብዳቤ የውሃ ሽታ ሆነባቸው፡፡ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቅሬታቸውን ካቀረቡ ውስጥ አትሌት ኢሳያስ ዳታ «ፌዴሬሽኑ ምዝገባውን ያካሄደበት ምክንያት ሯጮችን ህጋዊ ለማድረግ ነበር፡፡ የመወዳደሪያ ቁጥሩን ስገዛ መታወቂያ አሳይቼ ቢሆንም በሩጫው ቀን መታወቂያ ይዘህ መምጣት አለብህ የሚል ትዕዛዝ አልሰጡኝም›› በማለት ይገልጻል፡፡
ሌላው ቅሬታ አቅራቢ አትሌት ሳዲቅ ምስጋናውም «ማንነትህን የሚገልጽ መታወቂያ አሳይ ሲሉኝ መታወቂያ የለኝም፣ የፓስፖርቴን ፎቶ በስልኬ ላይ አንስቼዋለሁ፤ እዩትና ፍቀዱልኝ፣ በኋላ መታወቂያዬን አምጥቼ ታረጋግጣላችሁ ብዬ ብለምናቸው አሻፈረኝ አሉ›› ሲል ለዝግጅት ክፍላችን ተናግሯል፡፡ ሲመዘገብ በውድድሩ እለት መታወቂያ ይዞ እንዲመጣ እንዳልተነገረውም ጠቁሟል ፡፡
«ስለ ውድድሩ ደንብ በበቂ ሁኔታ ግንዛቤ ሳያስጨብጡን መቅጣታቸው ያሳዝናል» ያለው አትሌቱ፣ በየ5 ኪሎ ሜትሩ ምልክት እየተደረገ መሮጡንም ነው የሚናገረው፡፡ የውድድሩ አጠቃላይ ምስል መቀረጹን የጠቀሰው አትሌት ሳዲቅ፣ ምስሉን በማየት ቅሬታቸው በአፋጣኝ ታይቶ ምላሽ እንዲሰጣቸውም ነው የጠየቀው፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ የአትሌቶቹን ቅሬታ መሰረት በማድረግ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን አነጋግሯል፡፡ ጀርመን ሀገር የአሰልጣኝነት ስልጠና የወሰዱት ኮማንደር ዓይናለም አዳነ በአትሌቲክስ አሰልጣኝነት እና ዳኝነት ከ40 ዓመታት በላይ ሰርተዋል፡፡ እንደ ኮማንደር ማብራሪያ ከሆነ በየክልሉ የተለያዩ ውድድሮችን ለመዳኘት ሲንቀሳቀሱ መኖራቸውን ያስታውሳሉ፡፡
አትሌቲክስ ስፖርት ላይ በርካታ ማጭበርበሮች እንደሚከሰቱ የተናገሩት ኮማንደሩ፣ በየትኛውም የአትሌቲክስ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ማንነትን የሚያሳይ መታወቂያ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ መታወቂያ የሌለው አትሌት ከተሳተፈ እንኳ ውጤቱ ሊያዝለት እንደማይገባ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማህበር መተዳደሪያ ደንብን ዋቢ አድርገው ያብራራሉ፡፡
በየትኛውም ውድድር ላይ በቀይ ካርድ የተሰናበተ አትሌትን እንኳ «ሩጫውን እጨርሳለሁ» ካለ በኃይል ማስወጣት እንደማይቻል የገለጹት ኮማንደር ዓይናለም፣ ሩጫውን ለመከታተል የመጡ ደጋፊዎችን በማክበር ብቻ ከትራኩ ከማስወጣት ይልቅ ሮጦ ጨርሶ ውጤቱን አለመያዝ ህጋዊ አሰራር መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡ « በየውድድሩ ላይ የሚመጡ ተመልካቾች የአትሌቲክስ ህጉን በደምብ ስለማያውቁት ተወዳዳሪን ከማስወጣት ይልቅ ሮጦ ጨርሶ ውጤት አለመያዝ ተመራጭ ዘዴ ነው፡፡ በፔፕሲ ማራቶን ውድድር ላይም የተከሰተው ይኸው ነው፡፡ ለተከሰተው ችግር ኃላፊነት መውሰድ ያለባቸው ክለቦች እና በግል የተወዳደሩ አትሌቶች ብቻ ናቸው፡፡ ፌዴሬሽኑ ለዚህ ውድድር በሚል ያዘጋጀው ደንብ ይኖረዋል፡፡ ደንቡን መሰረት አድርገው እንደሚሰሩ እተማመናለሁ፡፡» በማለት አትሌቶቹ የጠየቁት « ውጤታችን ይያዝ» ጥያቄው ህጋዊ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ለረጅም ዓመት በዳኝነት እና በአሰልጣኝነት ያገለገሉት ኮማንደር ዓይናለም የትኛውም ውድድር ሲካሄድ ቀደም ብሎ ለአሰልጣኞች እና ዳኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም እንደሚዘጋጅ ጠቅሰው፣ የትኛውንም ውድድር ለማዘጋጀት ለአሸናፊዎቹ ሽልማት ከመስጠት ባሻገር በተወዳዳሪዎች ላይ ለሚደርሰው የትኛውም ጉዳት ኃላፊነት እንደሚወስድም ነው የገለጹት፡፡ በዚህ መልኩ በደንቡ ላይ የተቀመጠውን መስፈርት ሳያሟላ ወደ ውድድር የገባ አትሌት ለሚደርስበት ጉዳት አዘጋጆቹ ተጠያቂ እንደማይሆኑም ኮማንደር ዓይናለም ተናግረዋል፡፡
« በብዙ ውድድሮች ላይ አትሌቶች መታወቂያ ሲጠየቁ ረስተን ነው፡፡ ወይም ደግሞ መታወቂያ ይዛችሁ ኑ የሚል መልዕክት አልተነገረንም ሲሉ እንሰማለን፡፡ ሲጀመር መታወቂያ ይዛችሁ ኑ ባይባልም መታወቂያ መያዝ እንዳለባቸው ጠፍቷቸው አይደለም፡፡ ግማሹ ረሳሁ ግማሹ አልሰማሁም ሊል ይችላል» ያሉት ኮማንደር ዓይናለም፣ይብዛም ይነስም ሰሞኑን ለተከሰተው ችግር ግን ተጠያቂዎቹ ራሳቸው ተሳታፊዎቹ እንጂ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ኮማንደር ዓይናለም አክለውም ሰፊ ዝግጅት አድርጎ ለመሮጥ የመጣ እና አውቆም ይሁን ሳያውቅ መታወቂያውን ረስቶ ለመሳተፍ የመጣ አትሌት ከውድድር ከሚታገድ ይልቅ ሩጫው ላይ ተሳትፎ አቋሙን እንዲፈትሽ መደረጉ በራሱ ትልቅ ትብብር መሆኑን ጠቅሰው፣ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ አትሌትን ማሳተፍ ደግሞ ሌላ ተጠያቂነትን የሚያመጣ ብልሹ አሰራርን የሚያሰፍን በመሆኑ የፌዴሬሽኑ ውሳኔ አስተማሪ እና ህግን መሰረት ያደረገ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ህግ ሀገር አቋራጭ ውድድር ሲካሄድ ሯጮቹ በሚያልፉባቸው ቦታዎች ሁሉ በርካታ ዳኞች እንደሚመደቡ የገለጹት ኮማንደር ዓይናለም፣ በየ5 ኪሎ ሜትሩ ምልክት ቢደረግም በመሀል ዳኞችን አዘናግቶ ሾልኩ ሊገባ የሚችል አትሌት ስለሚኖር ከመነሻው መኖር አለመኖሩን በማረጋገጥ ውጤቱ እንደሚሰረዝም ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቴክኒክ ኦፊሰር አቶ አንዱዓለም ያየህይራድ በበኩላቸው ለፔፕሲው ሀገር አቋራጭ ውድድር ጥር 14ቀን2009ዓ.ም ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር መክረው ደንብ ማውጣታቸውን ገልጸው፣ በደንቡ መሰረት ምዝገባ አካሂደው ውድድራቸውን ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ በደንቡ አንቀጽ 4 ቁጥር 1 ላይ «ማንኛውም የክለብ ተወዳዳሪ የታደሰ ቲሴሪያ ይዞ መቅረብ አለበት፡፡ የታደሰ ቲሴሪያ ያላቀረቡ በውድድሩ ላይ መሳተፍ አይችሉም» እንደሚል የገለጹት ኦፊሰሩ፣በተመሳሳይ አንቀጽ 4 ቁጥር 2 ላይ ደግሞ በሁለት ቡድን ተመዝግቦ የተገኘ ተወዳዳሪ ውጤቱ እንደሚሰረዝ እና በተጨማሪ በውድድሩ ላይ ለተፈጠረው ችግር በደንቡ መሰረት አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወሰድበት በግል መቀመጡን ይናገራሉ፡፡
በአንቀፅ4 ቁጥር 3 ላይ ደግሞ ማንኛውም የግል ተወዳዳሪ የአዲስ አበባ ነዋሪነቱን የሚገልጽ መታወቂያ ይዞ በመቅረብ መመዝገብ እና መወዳደር እንደሚችልም በግልጽ መቀመጡን አቶ ዓንዱዓለም አመልክተዋል፡፡
በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 5 ቁጥር 3 ላይ ደግሞ የተወዳዳሪዎች ስም ጥሪ ከውድድሩ መጀመር 45 ደቂቃ ቀደም ብሎ እንደሚካሄድ በግልጽ መቀመጡን የጠቆሙት ኦፊሰሩ፣ በስም ጥሪው ውስጥ ያልተካተተ አትሌት ተወዳድሮ ቢገኝ ያስመዘገበው ውጤት በህጉ መሰረት እንደሚሰረዝ በዝርዝር መቀመጡን የመተዳደሪያ ደንቡን ዋቢ አድርገው ያብራራሉ፡፡ በውድድሩ ደንብ ላይ ግልጽነት ለመፍጠር ዓርብ ጥር 26ቀን 2009ዓ.ም ከተለያዩ ክለቦች ጋር ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ አንዱዓለም፣ በውድድሩ እለት መታወቂያቸውንና ቲሴሪያቸውን ይዘው ያልቀረቡ አትሌቶች መሳተፍ እንደማይችሉ በዚህች አናሳ ስህተትም ውጤታቸው እንዳይሰረዝ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጠቁመዋል፡፡
« ወደ ስም ጥሪ ስንገባም መረጃ ያላቀረቡ አትሌቶች መወዳደር እንደማይችሉ ነግረናቸዋል፡፡ ዳኞቹ ምልክት አድርገውባቸው ህጋዊ መረጃ ያቀረቡ ብቻ እንዲሳተፉ አድርገን ውድድሩን አስጀምረናል» ያሉት ኦፊሰሩ አቶ አንዱዓለም፣ በውድድሩ ማጠናቀቂያ ላይ ግን እውቅና ያልተሰጣቸው እና መስፈርቱን ያላሟሉ አትሌቶች መሳተፋቸውን መመልከታቸው እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ውድድሮች ሲዘጋጁ ውድድሩን ሊያበላሹ፣ ሌላ ተልዕኮ ይዘው የሚመጡ አትሌቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ ጠንካራ የማጣራት ሥራ እንደሚሰራ የተናገሩት አቶ ዓንዱዓለም ፌዴሬሽናቸውም የዓለም አቀፉን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የሀገር አቋራጭ ሩጫ ህጉን መሰረት አድርጎ የአትሌቶቹን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በውድድሩ ላይ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው የኤልሚ ኤሎንዶው ዓለማየሁ መኮንን አሰልጣኝ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን ብንጠይቅም ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባካሄደው 21ኛው የፔፕሲ ማራቶን ውድድር ላይ መጠነኛ ግርግር መፈጠሩ አይዘነጋም፡፡ ለግርግሩ መነሻ ግን በፌዴሬሽኑ የውድድር መተዳደሪያ ደንብ ላይ የተቀመጠውን ህግ በጣሱ አትሌቶች መሆኑ ባለሙያዎቹ አረጋግጠዋል፡፡ ፌዴሬሽኑም የቅሬታ አቅራቢዎቹን አትሌቶች ጥያቄ እንደማይቀበል እና ለችግሩ መፈጠር ምክንያት ራሳቸው በመሆናቸውን ኃላፊነቱን እንዲወስዱ ጠይቋል፡፡

 

ታምራት አበራ

Published in ስፖርት

 

ፕላኔታችንን በተለያዩ ዘርፎች የምትመራው አገረ አሜሪካ አርባ አምስተኛ ፕሬዝዳንቷን ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ካስገባች ሰነባብታለች፡፡ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ባለፀጋው ዶናልድ ትራምፕ ገና በሲመታቸው ማግስት አስገራሚ ውሳኔዎችን እያሳለፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ታዛቢን አፍርተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ባሳለፍነው ሳምንት የሰባት ሙስሊም አገሮች ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የጣሉት ክልከላ አነጋጋሪ እንደሆነ ዘልቋል፡፡ የአወዛጋቢውን መሪ ጉዳይ ለአፍታ ገሸሽ አድርጌ በኋሊት ምልሰት አስር መሪዎችን የሚያሻግር ትውስታ ላጋራችሁ፡፡

እርሳቸው 35ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ስማቸው ደግሞ ጆን ኤፍ ኬኔዲ ይሰኛል፡፡ ኬኔዲ በዓለም የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አሜሪካ ብቻ ሳትሆን መላው አለም ካያቸው ታላላቅ መሪዎች አንዱ ነበሩ፡፡ ብርቱ ሰው መሆናቸውም አብዝቶ ይነገራል፡፡ በአምስት አረፍተ ነገር በተጠናቀረ ደብዳቤ ሃርቫርድ ዩንቨርሲቲ እንዲቀበላቸው አሳምነዋል፡፡ (የእንደራሴዎች ምክር ቤት) የኮንግረስ አባልና የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ዘመን የተከፈላቸውን ደመወዝ በሙሉ ለበጎ አላማ ለግሰዋል፡፡ ስለ ጆን ኤፍ ኬኔዲ ድርሳን መዘርዘራችንን ከቀጠልን ጋዜጣው ሞልቶ መፅሃፍ ይወጣዋል፡፡ ታዲያ ምንድነው ስለ ኬኔዲ የምታወራን ትሉ ይሆናል!!!!

ጎበዝ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ የካቲት ስድስት 1962 እ.ኤ.አ መሆኑ ነው፤ ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ፒየር ሳሊንገር የተባለውን የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊያቸውን በቀጭን ትዛዝ ቢሮአቸው አስጠሩ፡፡

ሳሊንገር እንኩዋን መጣህ...እባክህ አንድ እርዳታ ፈልጌ ነበር ሲሉ ጠየቁት፡፡

ታዲያ ምን ችግር አለው ...ምን ልርዳዎ? በማለት ሰውዬው ትዛዝ ለመቀበል ተዘጋጀ፡፡

እስከ ነገ ጠዋት ድረስ አንድ ሺ ፔቲት አፕማን ሲጃራዎችን እንድታመጣልኝ ፈልጌ ነበር፤ ሲሉ አስጠንቅቀው ያዙታል፡፡ በትዛዛቸው የተገረመው ሳሊንገር የተባለውን ፍለጋ ከነጩ ቤተ መንግስት ይወጣል፡፡

 ፔቲት አፕማን ሲጃራ በ1844 እ.ኤ.አ በኩባ ሁለት ወንድማማቾች ያቋቋሙት በእጅ የተሰራ የሲጃራ ማምረቻ ድርጅት ነው፡፡ እናላችሁ የተባለውን ፍለጋ የወጣው ሳሊንገር እስከ ምሽት ድረስ የተባለውን ሲጃራ ይሰበስባል፡፡ ወትሮም ቢሆን ፕሬዚዳንት ኬኔዲ ሳሊንገርን ሲሊኩ የታዘዘውን እንደሚያመጣ ያውቁታል፡፡ ምክንያቱም ሳሊንገር ለኩባ ሲጃራ ያለው ፍቅር ከፍ ያለ ስለሆነ በዋሺንግተን ከተማ የሚገኙ ሲጃራ መሸጫዎችን አብጠርጥሮ እንደሚያውቃቸው ስለሚያውቁ ነበር፡፡

ሳሊንገር ...

በነጋታው ጠዋት ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ተመልሶ ይሄዳል፤ ቢሮው እንደገባ ከፕሬዚዳንቱ ቢሮ የተላከ የስልክ ጥሪ ይቀበለዋል፡፡ ጋሽ ኬኔዲ ነበሩ ...ሄሎ አሁኑኑ ቢሮ እንድትመጣ ብለው ስልኩን ዘጉት፡፡ ሳሊንገር ገና የነጩን ቤተ መንግስት እንቁላላማ ቢሮ በር ከፍቶ ከመግባቱ ችኮላ በሞላበት ድምፀት...ፒሬ ያን ጉዳይ እንዴት አደረከው ብለው ጋሽ ኬኔዲ ይጠይቁታል፡፡ ተቀመጥ እንኳን ያልተባለው ፒየር ሳሊንገር...አለቃ በሚገባ ተሳክቷል ሲል ይመልሳል፡፡

ፕሬዚዳንት ኬኔዲ በፈገግታ እየተሞሉ የጠረጴዛቸውን መሳቢያ ስበው ለሳሊንገር ረጅም ወረቀት ያቀብሉታል፡፡ ስማ ወዳጄ ከዚህ ሰአት ጀምሮ ማንኛውም የኩባ ምርት በአገራችን ውስጥ የተከለከለ ኮትሮባንድ መሆኑን የሚገልፅ የንግድ ማአቀብ ነው፡፡

...በል እንግዲህ እንደተለመደው ዉጣና  ...ለአሜሪካውያን ክልከላውን አንብብላቸው፡፡ ሲሉ ዳግም ትዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡ የተባለውን ለአለም ሊያረዳ፤ ፒየር ሳሊንገር ጋዜጠኞችን ሲጠራ ያኔ ወጣት አሜሪካውያን በትዊስት ዳንስ ወገባቸውን እየፈተኑ ነበር፡፡ አሜሪካውያን ጨረቃ ላይ ሰው አላሳፈሩም...ያኔ ያኔ የዛሬ 55 አመት፡፡

ዘመን ነጉዶ ጊዜ አልፎ ... ዛሬ ላይ ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ የፊደል ካስትሮ ሶሻሊስታዊ ስርአትን ለማሽመድመድ የጣሉትን የንግድ ማአቀብ ተቺዎች አፍ ሲወድቅ የማይረባ ፖሊሲ አስብሎታል፡፡ ለፊደልና ወንድማቸው ራውል ካስትሮ የተመዘዘው የኬኔዲ ሰይፍ ተራ ኩባውያንን በድህነት ቀልቷል፡፡ ኩባ እስከ 2012 እ.ኤ.አ በዚህ መአቀብ ምክንያት ወደ አንድ ትሪልዮን ዶላር ተነፍጋለች፡፡

 ጋሽ ኬኔዲ ለራሳቸው የሱስ መሻት ሲጃራቸውን አስገዝተው እያጨሱ በሰው ተገድለው ሞቱ፡፡ ያልሞተው ማአቀባቸው ብዙ የኔ ቢጤዎችን ፈጥሮ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ኖሮ አርጅቷል፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦባማ ሃቫና ሄደው ቡቱቶውን ቀዳደዱት እንጂ፡፡

...ዘመን ተለውጦ ጋሽ ትራንፕ ጋር ደረሰና የኬኔዲን ሲጃራ ወደ ስደተኝነት ለወጠው፡፡ ትራንፕ ሆዬ ለራሳቸው ሶስተኛ ሚስታቸውን ስደተኛዋን ካገቡ በሁዋላ ስደተኛ ወደ አሜሪካ ዝር እንዳይል ማለታቸው ...ግርም ከማለት አልፎ ይገራርማል፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ እ.ኤ.አ በ2002 የሜላንያን የትውልድ አገር ስሎቬንያን ለሶስት ሰአታት ይጎበኛል፡፡ እሷን ከመተዋወቁ ከሁለት አመት ቀድሞ መሆኑ ነው፡፡ ታዲያ አገር ብቻ አልጎበኘም የአገሪቷን መለሎም ማግባት ተመኘ፤ ሜላንያ ክናውስን ጠቀለላት፡፡ የሜላንያ አባት የስሎቫኒያ ሶሻሊስት ፓርቲ አባል ነበሩ፡፡ ሜላንያ ትራንፕ የአሜሪካን አፈር የረገጠችው በ1997 እ.ኤ.አ ነው፡፡ ለሞዴልነት ስራ ነው የተስፋይቱን ምድር የረገጠችው፡፡ አሜሪካ በስደተኝነት የገባችው ሴት የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት መሆን ችላለች፡፡ አቦ ይመቻት፡፡ ሰው የሚሰደደው እንዲያልፍለት አይደል እንዴ!!!!!...እንኳን አለፈላት ነው የሚባለው፡፡ እረ ሌላም ይጨምርላት፡፡

የሚገርመው የባልየው ነው፡፡ የመጀመሪያ ባለቤቱ የቼክ ሪፐብሊክ ዜጋዋ ኢቫና ትራምፕ ነች፤ ሶስተኛዋም ሜላንያ ትራምፕ ስሎቬኒያዊ፡፡ ከስደተኛ ትደር መስርቶ ከስደተኛ ጀርመናዊ አያት ተወልደው ‹‹ስደተኛ አይነ ውሃው አያምረኝም›› ማለት ምን የሚሉት ነው፡፡ ታሪክ እራሱን መለዮ ቀይሮ ደገመ ከማለት ውጪ፡፡ ፐሬዚዳንት ኬኔዲ ለራሳቸው ሲጃራቸውን ሸምተው የኩባ ሲጃራም ሆነ ሌላ ሸቀጥ ‹‹ክልክል ነው›› ብለው ማአቀብ ጣሉ፡፡ ትራምፕ ደገሞ ሰሞኑን ከስደተኛ ሚስቶች ተጋብተውና ተዋልደው....ከስደተኛ ቤተሰባዊ ሃረግ ተገኝተው የሰባት ሃገራትን ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ አገዱ፡፡ እኔ ሲመስለኝ ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ እና   ዶናልድ ትራምፕ ለአሜሪካ ህዝብ እንዲህ ያሉት ይመስለኛል...ለራሴ ይዣለሁ...ላንተ አልጨነቅም፡፡

ለሟች (ጆን ኤፍ ኬኔዲ) አፈሩን ያቅልላቸው እላለሁ፡፡ ሙት ወቃሽ መሆን ሳይሆን ከሞተ ታሪክ መማርና ማስተማር ይበልጣል፡፡ ጎበዝ በቁማቸው ... በቁማችን እየተወዛገቡ ለሚያወዛግቡን ዶናልድ ትራምፕ ግን የምላቸው አለኝ፡፡ በነገራችን ላይ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦባማ በድህረ ፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው የመጀመሪያ ሳምንታት ውብ የመዝናኛ ደሴቶችን እያካለሉ የፖለቲካ ‹‹አንጎቨራቸውን›› ሲያላቅቁ ሰንብተዋል፡፡ ወዲህ ደግሞ ገና በስልጣናቸው ዘመን ማለዳ  ትራምፕ ፍሎሪዳ በሚገኝ የግል እርስታቸው ‹‹ማራ ሎጎ›› በተሰኘው ውብ ክለብ ሲፍታቱ (ለስልጣንም ጫጉላ አለውንዴ?) ከርመዋል፡፡

እኛም እንዴት ነው ነገሩ፤ እኚህ የሁለት ዓለም ሰዎች በየፊናቸው የመንፈስ ቀለቡን ተያያዙትሳ? ብለን ብንጠይቅ አይገርምም፡፡ ለነገሩ ኦባማ ከስምንት ዓመት በፊት ወደ ነጩ ቤት ይዘው የገቡት ደማቅ ጥቁር ፀጉር ሲወጡ የሽሮ ሜዳ አገር ልብስ መስሎ ነው፡፡ በመሆኑም መዝናናታቸውን በቅናት መንፈስ አናየውም፡፡ ወዳጄ የነጩ ቤት ወንበር የአንድ ነጠላ አገር ጉዳይ አልፎ የዓለም ፖለቲካ መዘወሪያ ሳሎን በመሆኑ ለውጡ ባይገርምም የትራምፕ ቀድሞ መዝናናት ግን ‹‹ፀጉሬ እንደሆነ አንዴ ግራጫ ሆኗል›› የሚሉ አስመስሏል? በእርግርጥ መዝናናት ደግ ነው።መዝናኛው ከተገኘ፡፡ ‹‹ማራ ሎጎ›› የሚለው ቃል በእስፓኝ ቋንቋ በሃይቅና ባህር መካከል ያለ ቦታ ማለት ነው፡፡ ወይኔ...እንዴት የሚያምር ቦታ እንደሆነ በቀልባቹ ሳሉት...ኡ..ኡ... ኡፍፍፍፍፍፍ ቦታው ሲያምር፡፡

ታዲያ እዚህ የሚያምር ቦታ ሆነው የማያምር ጉዳይ በትውተር ሰሌዳቸው ሲሞነጫጭሩ (የስንቱን ጭንቅላት በነገር እንደሞነጫጨሩት ልብ ባሉት) የከረሙት ጋሽ ትራምፕ እንደ ማራ ሎጎ ክለቦች በሃይቅና ባህር መካከል ያለ መሬት መሆን አይችሉም፡፡ ሁለት ምርጫ አለዎት፤ አንድም ወደ ሃይቁ መጥለቅ ወይም ወደ ባህሩ መስጠም፡፡ ሁለቱም ውስጥ በአንድ ጊዜ መዋኘት አይቻልም፡፡ አንዱን ይምረጡ።በፕላኔታችን ላይ በተቀመጠሎት ክፍት ቦታ ላይ ፍቅር ወይስ ጥላቻን ያስገባሉ፡፡

ምርጫው የእርሶ ነው፡፡ እኔ ግን፤ ከውሳኔዎት በፊት የጋሽ ጥላሁን ገሰሰን ‹‹በየት ነው መንገዱ?›› የምትለዋን ዜማ ከስቴዲዮም ዙሪያ አስተርጓሚ ቀጥረውም ቢሆን ዜማዋን ኮምክመው ቢወስኑ... ውሳኔዎት አዱኛን ፎንቃ...በፎንቃ...ከማድረግ አልፎ ፍቅር መግቦት አለማችንን ያማረች ያደርጋታል የሚል ቁርጥ...ስምጥ...ጥልቅ እምነት አለኝ፡፡

በየት ነው መንገዱ?

እባካቹ ሰዎች ውሰዱኝ ስትሄዱ

ፍቅር ጋር መድረሻ በየት ነው መንገዱ

እሩቅ ነው ወይስ ቅርብ መኖሪያ መንደሩ

ግድ የለኝም እኔ ውሎ ለማደሩ

ያምራል ወይ በቅርፁ የፍቅር አዳራሽ

ኗሪ ቤት አለው ወይ  ወይስ ይሆን ፈራሽ

ዙሪያ አጥር አለው ወይ ወይስ ነው ወይ ሜዳ

ቦታስ ትርፍ አለው ወይ ማረፊያ ለእንግዳ

ጥያቄ እስቲ ላቅርብ እንዲያው ለነገሩ

በየት በኩል ይሆን የፍቅር ሀገሩ

ምን አይነት ነው ከቶ መውረጃና መውጫው

የፍቅር ማረፊያ ዋና መቀመጫው

የታወቀ ነው ወይ ጠቅላላ ታሪኩ

ቤቱስ ለመሆኑ ምን አይነት ነው መልኩ

ፍቅርን ተመልክቼ ከልቤ እንዳደንቀው

በዝርዝር አስረዱኝ መንገዱን ልወቀው

......መልካም ማሰብ ሙዴ ነው!......

 

ራጁ መሀመድ

Published in መዝናኛ

የዛሬው ‹‹የህይወት እንዲህ ናት›› አምድ እንግዳችን ከ20 በላይ መፅሃፍትን ለተደራሲያን ያቀረቡ፣ በተለያዩ የህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፉ እና አሁንም ከሕይወት ጋር ግብ ግብ የገጠሙ እና ነገ የተሻለ እንዲሆን የሚጓጉ ጎልማሳ ናቸው፡፡ ከሕይወታቸውና ተሞክሯቸው እንሆ! መልካም ንባብ፡፡

ውልደት እና ዕድገት

በወቅቱ ከሃምሳ የማይበልጡ  አባወራዎች በሚኖሩባትና ደቡብ ወሎ በምትገኘው  ቀይ አፈር በ1967 ዓ.ም አንድ  ህፃን ተቀላቀለ፡፡ ነዋሪው  በእልልታ እንኳ ከእናትህ ማሕፀን ወደ ምድር መጣህልን ብለው  በደስታ ተቀበሉት፡፡ ‹‹እከሊት ወለደች›› ተብሎም ተወራ፡፡በባህሉ መሰረት ገንፎ ተገንፍቶ ጎረቤትም ተጠርቶ ብስራት ሆነ፡፡ ይህ ህጻን ከፍ ሲል አቡሽ አሉት፡፡ ይኸው ያኔ እንደቀልድ የወጣለት ስም  ዛሬም ይጠራበታል፡:በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ በትምህርት ተገርቶም  ዶክተር የሚል ማዕረግ ተጎናፀፈ፡፡ በተወለደበት ቀይ አፈር አካባቢ እስከ አምስተኛ ክፍል ተምሯል፡፡

አቡሽ አንድ አመት ተኩል ሲሆነው  ነበር እናት እና አባቱ በድንገት የተለያዩት፡፡ እናም  አቡሽን የማሳዳግ ዕጣ  ፈንታ በአያቱ ጫንቃ ላይ አረፈ፡፡ እናም የእናት ጡት ብቻ ይመገብ  የነበረው  ሕጻን እናቱን እያስታወሰ በጣም ቀጨጨ፡:: አቡሽ ገና በህፃንነቱ ከተፈጥሮ ጋር ግብግብ ገጠመ፡፡ የጤናው ጉዳይ ፈተና ውስጥ ገባ፡፡  ሴት አያቱ ጠንካራ ነበሩ እና እንደምንም ምግብ አለማመዱት፤ እንደ አካባቢው ማህበረሰብም  በምክር እየገሩ አሳደጉት:፡ ፊደል መለየትና የቀለሙንም ዓለም በቄስ ትምህርት ቤት ጀመረው፡፡ በሂደትም  በዚያው  ቀይ አፈር መደበኛ ትምህርት ጀመረ፡፡

  ለትምህርት የደረሰው ሕፃን ገና በልጅነቱ የአጭር ርቀት እይታ ችግር (short sight) አጋጥሞት ነበር፡፡ በጊዜው ችግሩን የሚረዳው ሰው አልነበረም፡፡የሚቀመጠው   ኋላ ወንበር ላይ ነበር፡፡ ግድግዳው በጭቃ በተሰራው  ትምህርት ቤት ልጅነቱን አጣጣመ፡፡ በእይታ ችግር ምክንያት ሁለት ዓመት አንደኛ ክፍል መድገም  ግድ ሆነበት፡፡ የኋላ ኋላ የትምህርት ቤቱ ርዕሠ መምህር ችግሩን በመገንዛበቸው  ከፊት እንዲቀመጥ አደረጉት፡፡ አንደኛ ክፍል መድገሙ  ቀርቶ ሁለተኛ ክፍል እንዲገባ አደረጉት፡፡ እናም  በዚህ ሂደት ቀድሞ ያልተጣጣሙት አቡሽ እና ፊደል እጅና ጓንት ሆኑ፡፡ አቡሽ ፊደል ማጥመድ ጀመረ፡፡ ሌሎች ተማሪዎች ደግሞ  አቡሽ እንዲያስጠናቸው  በሚቻላቸው አቅም  ሁሉ  ያጠምዱት ጀመሩ፡፡

የአያት ልጅ ቅምጥል

አቡሽ ከልጅነት ጀምሮ ብዙም አይታዘዝም፡፡ የንባብ ልዩ ፍቅር ነበረው፡፡ይኸው ለዛሬ ማንነቱም  ፈር ቀዶለታል፡፡ አንባቢ  መሆኑም  የቀለም  ቀንድ  አድርጎታል፡፡ አልፎ አልፎ መረብ ኳስ ላይ ቋሚ  ተሰላፊ ሆኖ የስፖርት ብቃቱን ያሳይ ነበር፡፡ ብቻ በአያት ፍቅር ታጅቦ የሥኬትን መስመር ከማለዳው ተቆናጠጠ፡፡

ሚስጥራዊ ደብዳቤ

አቡሽ እስከ አምስተኛ ክፍል ቀይ አፈር ተማረ፡፡ ትምህርቱን ለመቀጠል በእግር ሦስት ሰዓት ተጉዞ ደጎሎ  የሚባል አካባቢ  ለመማር ተገደደ፡፡ ሲሄድ ለሳምንት የሚሆን ስንቅ ዳቦ አንዴ ተጋጋሮ ይሰጠዋል፡፡ ይህ ሕይወት ግን ፈታኝ ነበር፡፡ እናም አንድ ነገር ለማሰብ ተገደደ፡፡አባቱ አቶ አያሌው  ሃሳብና ናፍቆት እንዳነሆለላቸው  እና ልጃቸውን በጥሩ ሁኔታ ማስተማር እንደሚፈልጉ የልጃቸው  ጉዳይም እንቅልፍ እንደነሳቸው  አስመስሎ የፈጠራ ደብዳቤ ፃፈ፡፡

ደብዳቤውን ከአንድ መልዕክተኛ እንደተቀበለም ለአያቱ ነገራቸው፡፡ የሚያነበው  ሰው ስላልነበረ እራሱ በሚያሳዝን አባታዊ ቅላፄ ለአያቱ አነበበላቸው፡፡ ድርሰቱን ፅፎ እራሱ ተወናይ የሆነበት ደብዳቤ መሆኑን ዛሬ ላይ ሆኖ የኋሊት በትዝታ እየጋለበ ሲያስታውሰው  ንግግሩን ሳይጨርስ ሳቅ ይቀድመዋል፡፡እናም አያቱ ደብዳቤው  ሲነበብላቸው  በአይናቸው  እንባ እያቀረሩ ከራሳቸው ጋር ሙግት ገጠሙ፡፡ እንዴት ብለው ልጅን ከአባቱ ይለያዩ? ወዲህ ለማመን ተቸገሩ፡፡ እስከ ዛሬ ያልጠየቀህ አባትህ ዛሬ ስለምን ይህን ለማድረግ አሰበ ብለው ጠየቁት፡፡ ኋላ ላይ ግን ከውሳኔ ላይ ደርሰው  አቡሽን ወደ አባቱ ዘንድ ደሴ ሰደዱት፡፡

ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

አቡሽ እስከ 12ተኛ ክፍል በደሴ ተማረ፡፡ በብሔራዊ ፈተና አራት ነጥብ ስላመጣ በ1986 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀለ፡፡ አባት ልጃቸውን አስከትለው እየመከሩ ዩኒቨርሲቲ አደረሱት፡፡ አቡሽ ከፍተኛ ውጤት ስለነበረው የህክምና ትምህርት ክፍል እንዲማር ተደለደለ፡፡ ያኔ የሚኖረው ሳባ የሚባለው የተማሪዎች ህንጻ ላይ ነበር ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በትልቅ ህንፃ ላይ መኖሩ በወቅቱ አግራሞት እንደፈጠረበት ያስታውሳል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ሕይወትም ቀጠለ፡፡ የግቢው ማህበረሰብን መለማመድም እንዲሁ፡፡

አቡ፣ አቡሽ እና ፍቅር

አቡሽ የስድስተኛ ዓመት ተማሪ ሳለ አቡ  ከሚባል ጓደኛው ጋር ወደ ሽሮ ሜዳ ያቀናሉ፡፡ እናም አቡ ከአንዲት እንስት ጋር አቡሽን አስተዋወቀው፡፡ ግንኙነቱ ተጠናከረ፡፡ ጨዋታውም ደራ፡፡በአጋጣሚ  ፍቅር ተጀመረ፡፡የህክምና ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ አቡሽ ከተማሪነት ወደ ዶክተርነት ተሸጋገረ፡፡ ከጓደኛቸው ጋር እንኳን ደስ ያለህ ተባባሉ፡፡ ፍቅራቸው  ከተማሪነት እስከ ምረቃ ብሎም  እስካሁን ቀጥሏል፡፡

ከምረቃ በኋላ ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ወረዳ አረርቲ ጤና ጣቢያ ተመድበው  ስራ ጀመሩ፡፡ በመንግስት ተቋም ለአንድ ዓመት ለጥቂት ጊዜ ደግሞ በግል ጤና ተቋማት ተቀጥረው ሰሩ፡፡ ምንጃር ተመድበው  ሲሰሩ አገሬው በወቅቱ ፀብኛ በመሆኑ ቁስለኛ መብዛቱ ዛሬም ትዝ ይላቸዋል፡፡ ወዲህ የማህበረሰቡ እንግዳ ተቀባይነት አስገራሚ   ነበር፡፡ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ሺ 250 ብር ወርሃዊ ደመወዝ እየተከፈላቸው   የምንጃር ነጭ ጤፍ እንጀራ እየገመደሉ የቆዩበትን ጊዜ አይዘነጉትም፡፡ይሁንና ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ከአረርቲ ጤና ጣቢያ ጋር ፍቺ ፈፀሙ፡፡

በወቅቱ በተማሪነት ዘመናቸው ፍቅረኛቸው አዲስ አበባ ነበሩ፡፡ በጤናው ዘርፍ በቢዝነስ ላይ የመሰማራት እቅድም ነበራቸው፡፡ በተለይ ማህበረሰቡን በብዛት ለማግኘት በሚቻልበት ዘዴ ላይ ያስቡ ነበር፡፡ወደ ውጭ አገር የመሄድ ሃሳብም እንደደራሽ ውሃ ድንገት ይመጣ እና ወሰድ መለስ ያደርጋቸዋል፡፡ በመጨረሻም አዲስ አበባ በመምጣት ሜዲካል የምትባል ጋዜጣ መሰረቱ፡፡ የህክምና ምርምር ውጤቶችን እና ሌሎች ምንጮችን ዋቢ በማድረግ ብሎም የአገሪቱን የህክምና ደረጃና ጥበብ የደረሰበትንና በጤናው ላይ ያተኮሩ መረጃዎችን ለተደራሲያን ያቀርቡ ጀመር፡፡ በዚህ ሂደት ከበርካታ አንባቢያ አድናቆት እየጎረፉ መጠነኛ እውቅና አብሮ መጣ፡፡

‹‹…ሞቻለሁ ብዬ አስባለሁ…››

ሜዲካል ጋዜጣ በወቅቱ ደንበኞቿን የምታስተናግድበት አምድ ነበራት፡፡ በተለይ ማህበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ የገጠማቸውን በመታደግ ለበርካቶች ባለውለታ ነች፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ከአንባቢ የደረሰ ደብዳቤ እንዲህ ይላል፡፡‹‹ከ--- ወር ጀምሮ ሞቻለሁ ብዬ አስባለሁ… እባካችሁ ምከሩኝ›› የሚል ተማፅኖ ነበር የደብዳቤው መልዕክት፡፡ እናም ይህ አስገራሚ ደብደቤ ዶክተር አቡሽ አያሌውን እና የሜዲካል ጋዜጣ ቤተሰብን ግራ ያጋባል፡፡ ይህን ሰው በስልክ ማስረዳት ከባድ ነበር፡፡ ባለጉዳዩ በከፍተኛ ደረጃ ሃሳብ በማብዛት ወደ መጥፎ አዝማሚያ መግባቱን በመገንዘብ ከችግሩ ለማላቀቅ ተደጋጋሚ ምክር ሰጥተውት ወደ መደበኛ ሕይወቱ እንዲገባ ሞክረዋል፡፡

በ1997 ዓ.ም ደግሞ አንዲት ወደ አሜሪካ ለመሄድ የተዘጋጀች እንስት በደሟ ውስጥ ኤች አይ ቪ ቫይረስ በመገኘቱ ወደ አሜሪካ መሄዱ ህልም ሆነባት፡፡ ሁኔታው ሲያሳስባት መፍትሄ እንዲሰጧት ወደ ሜዲካል ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ደብዳቤ ጻፈች፡፡ በሦስት ቀን መልስ ካልተሰጣት እራሷን እንደምታጠፋ እና የወንድ ጓደኛ እንደምትፈልግ አሳሰበች፡፡ እናም ልጅቷን ቀድመው ማነጋገራቸውንና ሕይወቷን ማትረፉቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በኋላም ቫይረሱ በደማቸው ያለ ሰዎች አሜሪካ ወደ ግዛቷ መግባት እንደሚችሉ ስትፈቅድ ልጅቷ ከጓደኛዋ ጋር ሄዳለች፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ትዳር ፈላጊዎች የሚገናኙበትና የሚስተናገዱበት አምድ በመጀመርም በርካቶች ሦሶት ጉልቻ መስርተዋል፡፡ ይህ ለዶክተር አቡሽ አያሌው በሜዴካል ጋዜጣ የማይረሳ ትውስታቸው ነው፡፡

ከጋዜጣ ወደ መፅሃፍት

ዶክተር አቡሽ ከ20 በላይ መፅሃፎችን ፅፈዋል፡፡ የመጀመሪያ መፅሐፋቸው ‹‹የጂነስ ተማሪዎች ሚስጥር›› የሚለው ነበር፡፡ የሶስተኛ አመት ተማሪ ሆነው የጠነሰሱት ሃሳብ ነበር፡፡ በወቅቱ አጋዥ በማጣታቸው ስራ እስኪጀምሩ መፅሃፍ ማሳተም አልቻሉም ነበር፡፡ አብዛኞቹ በሜዲካል ጋዜጣ ይወጡ የነበሩ ፅፎች ወደ መፅሐፍነት ተቀይረዋል፡፡ በተለይ በስነ ልቦና፣ በቢዝነስ ስኬት፣ በጤና፣ በትምህርት፤ በዩኒቨርሳል ሳንይንስ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መፅፍትን በብዛት ለተደራሲያን አድርሰዋል፡፡ ፖለቲካንም በጨረፍታ ነካክተዋል፡፡

ካይዘን፤ ዘ ማይንድ፤ የጂነስ ተማሪዎች ሚስጥር የተሰኙት መፅሃፎቻቸው እያንዳንዳቸው ከ30ሺ በላይ ኮፒ ታትመዋል፡፡ አሁንም እነዚህ መፅሐፎች በየዓመቱ ከ5ሺ ኮፒ በላይ ይታተማሉ፡፡ በርካቶች መፅሃፉን አንብበው ህይወቴ ተቀይሯል የሚል አስተያየት መስጠታቸው ለበለጠ ስራ አነሳስቷቸዋል፡፡ በትውልዱ ላይም በትንሹም ቢሆን መልካም አሻራ ማስቀማጣቸውን ያመላክታቸዋል፡፡ መፅሃፍ ከቢዝነስ አኳያ አዋጭ ባይሆንም ለትውልድ እውቀት ማስተላላፍ ላይ ያተኮሩ በመሆኑ ደስታቸው ወደር የለውም፡፡

አዋቂነት ወይስ ታዋቂነት?

ዶክተር አቡሽ ‹‹የሰው ልጅ የተወለደው ችግር ፈቺ ሆኖ ነው፡፡ ችግሮች ከእኛ በላይ ከሆኑ እንጠፋለን አሊያም የትም አንደርስም›› ይላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ እውቀት ግድ ነው፡፡ ይህን ታሳቢ ያደረጉ እና ችግር ፈቺ የሆኑ ሳይንሳዊ መፅሃፎች ላይ አተኩረዋል፡፡ ድርሰታቸው በአብዛኛው ትምህርት ሊሰጡ በሚችሉ እና በትውልድ ውስጥ መልካም አሻራ ጥለው በሚያልፉት ጉዳዮች ላይ ማጠንጠናቸው ደስታቸውን ጥግ ያደርሰዋል፡፡

መፅሃፎቹ ገንዘብ ከማስገኘታቸው በላይ በቤተሰባቸው ላይ አዎንታዊ ጫና ፈጥሯል፡፡ እውቀት ከራስ ይጀምራል የሚለውን አስተሳሰብ በቤተሰባቸውም ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡ ዶክተር አቡሽ እናት እና አባታቸው ገና እርሳቸው ጨቅላ ሳሉ መለያየታቸው በእርሳቸው ዘንድ ትምህርትም፣ ጥንካሬም ብሎም ቁጭት ጥሎላቸው አልፏል፡፡ ከትዳር በፊት እና በትዳር ውስጥ ስለሚደረግ ሥነ ልቦናዊ ዝግጅም ዘማይንድ በሚል በመፅሃፋቸው በሚገባ አትተዋል፡፡ በመፅሀፎቹ ውስጥ የእኔ ድርሻ እውቀትን ማሳወቅ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ በሂደት ስራቸው አስተዋወቃቸው፡፡ እናም መጀመሪያ አዋቂ መሆናቸው ከአዋቂነት ወደ ታዋቂነት መንገድ እያመራቸው እንደሆነም ያምናሉ፡፡

ጉዞ ወደ ዲጅታል …

ሚዲካል ጋዜጣ ቀርታ ሜዲካል መፅሄት እየታተመች ነው፡፡ መፅሄቷ 20ሺ ኮፒ ትታተም የነበረ ሲሆን፤ አሁን ወደ አምስት ሺ ዝቅ ብላለች፡፡ የሰው አኗኗር ተቀይሯል፡፡ ሰው ከቴክኖሎጂ ጋር በየእለቱ መነጋገር በመጀመሩ በዲጅታል ዘመን ዲጅታል አስተሳሰብ ይዘው ደንበኞቻቸውን ለማግኘት ዝግጅት አጠናቀዋል፡፡ በቀጣይ ስድስት ወር ውስጥ ‹‹ዶክተር አቡሽ ዶት ኮም›› በሚል በዩቲዩብ ደንበኞቻቸውን ያገኛሉ፡፡

በዚህም ስራ ፈጠራን፤ የስኬት መንገድ፤ ወጣትነት እና ችግሮቻቸው እንዲሁም መፍትሄዎቻቸው ላይ ያተኮሩ አጫጭርና አስተማሪ መረጃዎች በድምጽ እና በምስል የመልቀቅ ሂደት ላይ ናቸው፡፡ በዚህም ሚሊዮን ተከታዮችን ለማፍራትና ተደራሽነትን ለማስፋት ብሎም ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል እንደሚጥሩ ይናገራሉ፡፡ 

ዛሬ እና ነገ

ፓወር ሃውስ የሚባል የስልጠና ማዕከል አላቸው፡፡ ለሆቴሎች፣ ለህክምና ድርጅቶች፣ ለፋብሪካዎች እና ለሌሎች ድርጅቶች አመራሮች እና ሠራተኞች ስልጠና ይሰጣሉ፡፡ ሲስተም ዲቭሎፕመንት ላይ ይሰራሉ፡፡ ጣፋጭ ቢዝነስ የተሰኘ ፕሮግራምም በፋና ኤፍ ኤም ያስተላልፋሉ ፡፡ በቀጣይም በፋና የቴሌቪዥን እስክሪን ብቅ ለማለትም በመነጋገር ላይ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት 25 ቋሚ እና 14 ጊዜያዊ ሠራተኞች አሏቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ዘላለም አብረዋቸው እንዲቆዩ አይፈልጉም፡፡ ይልቅስ ፍላጎታቸው ‹‹እሳት የላሱ›› የቢዝነስ ሰዎች እንዲሆኑ ነው፡፡ በሥራቸውም ላይ ጠንካራ እንዲሆኑ ሙያዊ እገዛ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ መንገድም በርካታ ሰራተኞችን ወደ ተሻለ ደረጃ አድርሰዋል፡፡ በቅርቡም ‹‹ዶክተር አቡሽ ዶት ኮም›› ላይ ሚሊዮን ተከታዮችን እና ሚሊዮን ሥራ ፈጣሪ ኢትዮጵያዊያን እና አፍሪካዊ ባለ ራዕይ ወጣቶችን ለማፍራት ይተጋሉ፡፡

የማያበራ ዕውቀት መሻት

ዶክተር አቡሽ አያሌው አጫጭር ስልጠናዎችን በመውሰድ የበለጠ ልምድ አዳብረዋል፡፡ ግን ስራቸውን የበለጠ ለማጠናከር መማር እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡ የቤተሰብ ጊዜ በመሰዋት ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እና የአሜሪካው ሊንከን ዩኒቨርሲቲ በጋራ በኢትዮጵያ በከፈቱት ተቋም በጥር 2009 ዓ.ም አራት ነጥብ በማምጣት የወርቅ ዋንጫ ወስደው በቢዝነስ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በቀጣይም እንደ አመቺነቱ በዚህ የትምህርት ዘርፍ ዶክትሬታቸውን የመማር ህልም አላቸው፡፡

ዶክተር አቡሽ በአፍሪካ ደረጃ የተማረ እና ምርጥ ሥራ አስፈፃሚ የመሆን ህልም አላቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም አንቱ ለመባል ይሻሉ፡፡ በትላልቅ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች የማስተማር እና አገራቸውን፣ አፍሪካን ብሎም ዓለምን የሚጠቅም ጥናት የመስራት ፍላጎት አላቸው፡፡

ፖለቲካን መፍራት ወይስ ማመዛዘን?

‹‹እኔ ሳይንሳዊ በሆነ መረጃ ላይ ተመስርቼ መናገር እፈልጋለሁ፡፡ ሳላውቅ መናገር በጣም እፈራለሁ›› ይህ የዶክተር አቡሽ አቋም ነው፡፡ በዚህ አቋማቸው አንዳንዶች የኢህአዴግ ደጋፊ ነህ ይሏቸዋል፡፡ በሌላ ጽንፍ ተቃዋሚ ነህ ሚሉም አሉ፡፡ ግን እርሳቸው ሁል ጊዜ ሚዛናዊ ንግግር መናገር ይፈልጋሉ፡፡  በአሁኑ ወቅት መሻሻልም ሆነ መጠናከር ያለበት ነገር እንዳለ ያምናሉ፡፡ ግን ፖለቲካ ላለመፍራታቸው ዶሴ መዘው መረጃ ያቀርባሉ፡፡ በቅርቡም ፖለቲካ ላይ ያጠነጠነ ‹‹የማያባሩ አብዮቶች›› በሚል መፅሃፍ ፅፈዋል፡፡ በአውሮፓ እና አሜሪካ አገር  ዘላቂነት  ያለው መረጋጋት እና እድገት ለምን እኛ ዘንድ አይኖርም በሚል የሚሞግት መፅሃፍ ነው፡፡  ድህነት እና ጦርነት ለምን የእኛ መለያ ይሆናል ሲሉም ነው የሚሞግቱት፡፡ በቀጣይም ይህ ሃሳባቸው የፀና ነው፡፡ በእርሳቸው እምነት ‹‹ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ያለው መሪ እና ማህበረሰብ›› ያስፈልገናል የሚለው ነው፡፡

ምስጋና እና ሽልማት

በኒዮርክ የሚገኘው ዩኒቨርሳል ፒስ ፌዴሬሽን የሠላም አምባሳደርነት ማዕረግ አበርክቶላቸዋል፡፡ ይህም የተሰጣቸው በአገሪቱ ውስጥ ለማህበራዊ ሕይወት ያበረከቱትን ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የበጎ ሥነ ምግባር አምባሳደር ሆነው ተሸልመዋል፡፡ በቅርቡም ከሠራተኞቻቸው የተበረከተላቸው የአድናቆት እና ምስጋና ስጦታ መቼም የማይረሳቸውና የእርሳቸውን አመራር ከምን ደረጃ እንዳለ የተገነዘቡበት እንደሆነ ይነገራሉ፡፡

ምክር

የህይወት ፍልስፍናቸው በሕይወትህ ደስ ብሎህ መኖርን መለማመድ አለብህ የሚል ነው፡፡ ለሁሉም ሰው ሕይወት ብልፅግና ነው፡፡ ብልፅግና ደግሞ በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በማህራዊ ሕይወት ስኬት ጭምር ነው፡፡ በማህበራዊ ሕይወት ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም ጠንካራ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ማህበራዊ ስኬት ብቻውን ጠንካራ አያደርግም፡፡ እኛ ልክ እንደ አውሮፓውያኑ ሁሉ ማደግ መበልፀግ እና የተድላ ሕይወት ሊኖረን ይገባል፡፡ እራሳችንን አሸንፈን ለሌላውም ተርፈን መኖር አለብን፡፡ የምንፈልገውን እና የሚያስፈልገንን ሁሉ ለማሟላት ሥራ ሳንንቅ እንስራ፡፡ የአክሱም ላሊበላ ዘመን ስልጣኔ እና ቆራጥነት ዛሬም ዳግም መለምለም አለበት፡፡ ስልጣኔ ገደብ ባይኖረውም ከታችኛው ወለል መውጣት አለብን ይላሉ፡፡ ከዶክተር አቡሽ አያሌው ሕይወት ልምድ እንደምትቀስሙ በማሰብ የሳምንት ሰው ይበለን፡፡ መልካም ሰንበት፡፡

 

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

Published in ማህበራዊ

በህገመንግስቱ አንቀፅ 44 ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ መንግስት በሚያካሂዳቸው ፕግራሞች ምክንያት የተፈናቀሉ ወይም ኑሯቸው የተነካባቸው ሰዎች ሁሉ በመንግስት በቂ ዕርዳታ ወደ ሌላ ቦታ መዘዋወርን ጨምሮ ተመጣጣኝ የገንዘብ ወይም ሌላ አማራጭ ማካካሻ የማግኘት መብት እንዳላቸው በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ልማት ህዝብን ያሳተፈ መሆን እንዳለበትም እንዲሁ በህገመንግስቱ ተደንግጓል፡፡ ልማቱ በሚከናወንበት አካባቢ ያለን ህብረተሰብ ማሳመን እና የልማቱ ተጠቃሚ ማድረግም የግድ ነው፡፡

ነገር ግን በኦሮሚያ ክልል የአርጆ ዴዴሳ እና በአማራ ክልል የጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢውን ህብረተሰብ ከመጥቀም ይልቅ በእጅጉ እየጎዱ መሆናቸውን የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በጥናት ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል፡፡ፕሮጀክቶቹ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ እንዳልተደረገላቸው ይነገራል፡፡ፕሮጀክቶቹ በሚገነቡበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ‹‹ልማቱ እኛን ያሳተፈ ሳይሆን ጭራሹኑ ለጉዳት ያጋለጠ ነው›› በማለት፤ በተለያዩ የህዝብ መድረኮች ላይ ድምፃቸውን ከማሰማት አልፈው ለህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

ተቋሙም የቀረቡ ቅሬታዎችን መሰረት አድርጎ ቡድን በማደራጀት በሁለቱም ክልሎች ምርመራ አካሂዷል፡፡ ምርመራው በቦታው ተገኝቶ በመመልከት፤ ቪዲዮ በመቅረፅ፤ ተጎጂዎቹን ቃለ መጠይቅ በማድረግ፤ የቀበሌ፣ የወረዳ፣ የዞንና የክልል አስተዳደሮችን እንዲሁም የሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማትንም በማነጋገር ተከናውኗል፡፡

የምርምራ ሂደትና ውጤት-በኦሮሚያ

     የምርመራ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ የአርጆ ዴዴሳ የስኳር ፕሮጀክት እና ለፕሮጀክቱ  የሚያገለግለው የመስኖ ልማት ግድብ የአራት ወረዳ ሰዎችን ለጉዳት አጋልጧል፡፡ በቦርቻ ወረዳ አስተዳደር 373 አርሶ አደሮች ንብረታቸው በትክክል ሳይቆጠር፣ ካሳ ሳይከፈላቸው፣ ምትክ መሬትም ሳይሰጣቸው ከመኖሪያ ቤታቸው እንደዋዛ ተፈናቅለዋል፡፡ ለአንድ አመት ከስምንት ወር በላስቲክ መጠለያ ድንኳን በመኖራቸውና የሚቀርብላቸው እርዳታም በቂ ባለመሆኑ ለተላላፊ በሽታና ለምግብ እጥረት የተጋለጡ ሲሆን፤ በዚህም 33 ህፃናት ሞተዋል፡፡ ስለመስኖ ግድብ ግንባታውና ውሃው አካባቢውን ቢያጥለቀልቅ እንዴት ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ባለመሰራቱ  ለግድብ ተብሎ የተሰራው ውሃ በመሙላቱ 4 ሰዎችና 64 የቤት እንስሳት በአዞ ተበልተዋል፡፡

በተጨማሪም 220 አርሶ አደሮች ካሳና ምትክ መሬት አልተሰጣቸውም፡፡ ለካምፕ መስሪያ በሚል ይዞታቸውን ያጡት 48 አርሶ አደሮችም ካሳ አላገኙም፡፡ ፕሮጀክቱን ለማስተግበር በሚል በደል የደረሰባቸው ሰዎች የጤና እና የትምህርት አገልግሎት እያገኙ አለመሆናቸውን የምርመራ ግኝቱ ያመለክታል፡፡ በቦረቻ ወረዳ ያሉ ነዋሪዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ለነገ ህይወታቸውም ትልቅ ጠባሳን ጥሎ የሚያልፍ መሆኑንም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

በሊሙ ሠቃ ወረዳ 289 አርሶ አደሮች በመስኖ ግድቡ ምክንያት ከይዞታቸው ተነስተው ለንብረታቸው ካሳ፣ ለይዞታቸው ምትክ አልተሰጣቸውም፡፡ 47 አርሶ አደሮች ደግሞ ካሳ ቢከፈላቸውም ምትክ መሬት አላገኙም፤ 67 አርሶ አደሮች የተሰጣቸው ምትክ የእርሻ መሬት ውሃ የተኛበት እና ለእርሻ ምቹ አለመሆኑን የእንባ ጠባቂ የምርመራ ቡድን አረጋግጧል፡፡

በበደሌ ወረዳም 358 አርሶ አደሮች የአካባቢው ነዋሪ እና የእርሻ መሬት ያላቸው ቢሆንም ከቦታው ሲነሱ ምትክ መሬት አልተሰጣቸውም፡፡ ሌሎች 170 አርሶ አደሮች ደግሞ በቋንቋ ትርጉም ስህተት ሳቢያ ካሳው ከሚገባው በላይ ዘግይቶባቸዋል፡፡ በጅማ አርጆ ወረዳ አስተዳደርም 45 አርሶ አደሮች ካሳ ያልተከፈላቸው ሲሆን 21 አርሶ አደሮች ደግሞ ምትክ መሬት አልተሰጣቸውም፡፡ በአጠቃላይ በክልሉ በፕሮጀክቱ ሳቢያ አንድ ሺ 638 አርሶ አደሮች የአስተዳደር በደል እንደደረሰባቸው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋሙ በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡

    የአርሶ አደሮቹ አስተያየት

በኦሮሚያ ክልል ኢሉ አባቦራ ወረዳ የሚኖሩት አቶ አብዲ ከዲር እንደሚናገሩት፤ በፕሮጀክቱ ከመኖሪያቸው ከተፈናቀሉ ሁለት ዓመት ሊሞላ ነው፡፡ በሸራ በተወጠረ መጠለያ ሲኖሩ ትንሽ ብር ቢሰጣቸውም አልቆባቸዋል፡፡ የተወጠረው ሸራም ፀሃይና ዝናብ ሲፈራረቅበት ቆይቶ አሁን መበጣጠስ በመጀመሩ ለሊት በብርድ እየተሰቃዩ ነው፡፡ ልጆቻቸው አይማሩም፡፡ በምግብ እጥረት ሰዎች እየተሰቃዩ እና እየሞቱ ነው፡፡ የእርሳቸውም ስምንት የቅርብ ዘመዶቻቸው ከተፈናቀሉ በኋላ በምግብ እጥረትና በህመም ለሞት በቅተዋል፡፡ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው እየጮሁ ቢሆንም መፍትሄ አላገኙም፡፡

በክልሉ በቦርቻ ወረዳ በኦግዳ አርባ አካባቢ የሚኖሩት አቶ አባ ከድር በበኩላቸው፤ የአርጆ ዴዴሳ ግድብ በመገደቡ ውሃው ወደ ኋላ ሲተኛ ማሳቸው በውሃ መጥለቅለቁን ይናገራሉ፡፡

‹‹ በሁለት ሄክታር ከግማሽ ለም መሬት ላይ ፍራፍሬዎችን ተክዬ ነበር፡፡ በተጨማሪ ማሽላ፣ ሸንኮራ፣ ጫት፣ ማንጎ እና ቡናን የመሳሰሉ ምርቶች ሙሉ ለሙሉ በውሃ ተጥለቅልቀውብኛል፡፡ በዓመት በአጠቃላይ ከ150 ሺ ብር ያላነሰ አገኝ ነበር። አሁን ግን ባዶዬን ቀርቻለሁ›› ብለውናል፡፡

ማሳቸው በውሃ የተጥለቀለቀው በ2007 ዓ.ም መሆኑን በማስታወስ ችግሩ የእርሳቸውን ህይወት ብቻ ሳይሆን የሚያስተዳድሯቸውን 12 የቤተሰቡን አባላት እየጎዳ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ አሁንም አካባቢው በውሃ የተጥለቀለቀ ሲሆን ጥያቄ ደጋግመው ቢያቀርቡም እናዘዋውራችኋለን ከማለት ውጪ፤ በተግባር የታየ ምንም መፍትሄ እየመጣ አለመሆኑን ይገልፃሉ፡፡

   የምርምራ ቡድን መፍትሄ

በህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የኦሮሚያ ቅርንጫፍ የምርመራ ዳይሬክተር እና የምርመራ ቡድኑ መሪ አቶ አድማሱ አበበ፤ ችግሩ አሁንም ያለ መሆኑንና ተጎጂዎቹ በመጠለያ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ሪፖርቱ የደረሳቸው የፌዴራል ተቋማት የተነጋገሩበት ቢሆንም ተጨባጭ እርምጃ አለመወሰዱን አመልክተው፤ ተጎጂዎቹ አሁንም ለተቋሙ የምርምር አካል እየደወሉ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

መጀመሪያውኑ ህብረተሰቡ የሚሰፍርበትን ሁኔታ ማጥናትና ማስፈር እንዲሁም እስከ ማቋቋም የዘለቀ ስራ መሰራት ነበረበት፡፡ ቀድሞ በጥናት ተመስርቶ አለመሰራቱ ዜጎችን በእጅጉ ጎድቷል፡፡ ከጥናቱም በኋላ ማንም ችግሩን ለመፍታት ቦታው ላይ አልተገኘም፡፡ የክልሉ መንግስት በድንኳን ያለውን ህብረተሰብ ለማንሳት መሬት አዘጋጅቻለሁ እያለ ነው፡፡ በተለይ ቅድሚያ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ህፃናትና አረጋውያን በቀጣይ ክረምት የባሰ ለአደጋ ሊጋለጡ ስለሚችሉ የእነሱን ህይወት ለማዳን ስኳር ኮርፖሬሽንም ሆነ የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሌላውም አካል ተረባርቦ እነዚህን ሰዎች በፍጥነት መጠለያ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በቅንጅት መስራት ይኖርባቸዋል በማለት መፍትሄ ያሉትን አቶ አድማሱ ተናግረዋል፡፡

በቅንጅት በሃላፊነት ስሜት ካልተሰራ ህብረተሰቡ በቀጣይ ክረምትም በድንኳን ይኖራል :: ህብረተሰቡም የበለጠ ይጎዳል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ በድንኳን ካሉ ተጎጂዎች በተጨማሪ በተበጣጠሰ መልኩ መሰራቱ ካሳ የሚሰጥበትን ሁኔታንም አዘበራርቋል የሚሉት አቶ አድማሱ፤ የጋራ ፅህፈት ቤት ተቋቁሞ፤ ያላቸውን ንብረት መዝግቦና ካሳ የሚከፈላቸውንና የማይከፈላቸ ውን ለይቶ በህግ መሰረት መስጠት ሲገባ ለአርሶ አደሮች በተቆራረጠ መልኩ  እንዲከፈል አስገድዷል፡፡ ይህም ቅሬታ ፈጥሯል፡፡ አንዳንዱ ካሳ የሚገባው ሆኖ ካሳ ያላገኙ አሉ ብለዋል፡፡

አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችል ይሆናል ተብለው የሚገመቱ ቦታ የለንም በሚል መነሳት እያለባቸው ያልተነሱ፤ አንድ ሺ 500 ሰዎች መኖራቸውን እና ለእነዚህም ከወዲሁ በቅንጅት ካልተሰራ አደጋው የበለጠ የከፋ እንደሚሆንም ነው የሚናገሩት፡፡ ሃላፊነቱ የኔ አይደለም በማለት ወደ ሌላ ከመግፋት ይልቅ የጋራ ፅህፈት ቤት በማቋቋም መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የምርምራው ሂደትና ውጤት-አማራ ክልል

የአማራን እና የቤንሻንጉል ክልልን አማክሎ 75ሺ ሄክታር ማሳን የሚሸፍነው የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ላይም 36 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ካሳ ያልተከፈላቸው መሆኑን፤ 213 አርሶ አደሮች በህጉ መሰረት ምትክ እርሻ መሬት እንዳልተሰጣቸው፤ 87 አርሶ አደሮች ደግሞ በምትክነት የተሰጣቸው መሬት ምርታማ ያልሆነ፤ ድንጋያማና ተዳፋት የበዛበት እና ለእርሻ የማይውል መሆኑን የዋና እንባ ጠባቂ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቀንአ ሶና ያመለክታሉ፡፡

ሁለት ሺ 535 አርሶ አደሮች ከነባር ይዞታቸው ጋር ተመጣጣኝ መሬት ያልተሰ ጣቸው መሆኑን፤ 415 አርሶ አደሮች የተሰጣቸው እርሻ መሬት ከመኖሪያ ቤታቸው 60 ኪሎ ሜትር እንደሚርቅ፤ ለ198 ሰዎች የይዞታ ማረጋገጫ አለመሰጠቱን እና 158 ተነሺዎች በደንቡ መሰረት 500 ካሬ ሜትር የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

በቂ የንፁህ መጠጥ ውሃ ግንባታ፤ የመብራት አገልግሎት፤ የጤና እና የትምህርት ተቋማት እንዲሁም ለአርሶ አደሮች ተገቢው የኑሮ አማራጭና ድጋፍ አለመኖሩ አርሶ አደሮቹን መልሶ ለማቋቋም የተሰራው ስራ ችግር ያለበት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ የተቋሙ መርማሪ ቡድንም ይህንን እንዳገኘ አቶ ቀንአ ተናግረዋል፡፡

የልማት ተነሺዎች በተገባላቸው ቃል መሰረት የመስኖ ተጠቃሚ አለመሆናቸው፤ በሚፈለገው ደረጃ ለአካባቢው ህብረተሰብ የስራ ዕድል አለመፈጠሩንም ነው ሃላፊው ያመለከቱት፡፡ በእነዚህ ሰዎች ላይ ለደረሰው በደል፤ የክልል ሃላፊዎች ለስኳር ኮርፖሬሽን እና ለውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተቋሙ ግኝቱንና የመፍትሄ ሃሳቡን አቅርቧል፡፡

በአማራ ክልል ጃዊ ወረዳ አርጋቦ ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አናጋው ዋሌ እንደተናገሩት፤ በጣና በለስ ምክንያት በ2004 ዓ.ም አርሶ አደሩ ተፈናቅሏል፡፡ እስከ አሁን መሬት ያላገኙ፤ የከብት መዋያ የግጦሽ መሬት ያጡ ብዙ ናቸው፡፡ ምትክ መሬት ቢሰጥም ያለጥናት በዘፈቀደ የተሰጠ ሲሆን፤ መሬቱ የማያበቅል ለእርሻ የማይሆን መሬት በመሆኑ ተነሺዎቹ እየተጎዱ ነው፡፡

ለተነሺዎቹ ምን መደረግ እንዳለበት በወቅቱ መንግስት ማጥናት ነበረበት፡፡ ቦታ ሲሰጥም በረሃ ላይ ለእያዳንዱ አርሶ አደር አንድ ነጥብ አምስት ሄክታር ብቻ ነበር፡፡ ይህ ለበረሃ መሬት በቂ አይደለም፡፡ የካሳ ክፍያውም ለአንዳንዱ ተከፍሎ፤ ሌሎች ካሳ ሳይከፈላቸው ተዳፍኖ የቀረባቸው አሉ፡፡ የመንግስት ልማት ነው በሚል መሬቱ እንዲሁ ተገቢውን ካሳ ሳይከፈል የሚወሰድበት ሁኔታ አለ ብለዋል፡፡ መሬት አሰጣጡም የተዘበራረቀ መሆኑን እና ለክልል ጥያቄ ማቅረባቸውን አመልክተው፤ አዳማጭ አጥተው መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል የባህርዳር ቅርንጫፍ እንባ ጠባቂ ተቋም የምርመራ ዳይሬክተር የሆኑትና ቡድኑን የመሩት አቶ ሃብታሙ ታደሰ እንደሚናገሩት፤ ጣና በለስን አስመልክቶ ምርመራው የተሰራው ጥቅምት ላይ ነበር፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮ በየደረጃው ለሚመለከተው አካል ሪፖርቱ ቀርቧል፡፡ ልማት መነሻውም ሆነ መድረሻው ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን በጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት ላይ በመልሶ ማቋቋምም ሆነ ከልማት ተጠቃሚነት አንፃር ችግር መኖሩን በጥናት ተረጋግጧል፡፡

ምትክ መሬት አሰጣጥ ላይ በዋናነት የሚመለከተው ክልሉን በመሆኑ ለዛው ሪፖርቱ ቀርቧል፡፡ የሚመለከተው የገጠርና መሬት አስተዳደር ቢሮ በየተዋረዱ ያሉ ተቋማት በተለይ የጃዊ ወረዳ ፅህፈት ቤት መሬት የመስጠት ሂደቱ የሚመለከተው እርሱን በመሆኑ የድርጊት መርሃ ግብር በማውጣት በጊዜ ገደብ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ምትክ መሬት ያላገኙት ሰዎች መሬት እንዲያገኙ እንዲሰሩ የተነገራቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማያበቅል መሬት የተባለው የተረጋገጠው በግብርና ባለሙያዎች ሲሆን፤ ተደፋታማነቱ ከፍተኛ በመሆኑ ተለዋጭ መሬት እንዲሰጣቸው የመፍትሄ ሃሳብ ማስቀመጣቸውንም ተናግረዋል፡፡ የመሬት ችግር ካለም በህጉ መሰረት ዘላቂ መፍትሄ  የሚበጅበት ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ ክልሉ በተቀመጠ የጊዜ ገደብ ውስጥ ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ ካልወሰደ በአዋጁ መሰረት የሚመለከታቸውን የስራ ሃላፊዎች ተጠያቂ የማድረግ ሁኔታ ይኖራል ብለዋል፡፡

ነገር ግን ችግሩን ተቀብለው መግባባት ላይ በመደረሱ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ ይገኛል ብለው እንደሚጠብቁም ይናገራሉ፡፡ ልማቱን ለማስጠበቅ ከህብረተሰቡ ጋር ተስማምቶ የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጠር ማድረግ ካልተቻለ ዘላቂነት ስለማይኖረው ቢያንስ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ በየደረጃው ከሚመከታቸው አካላት ጋር መነጋገራቸውን ተናግረዋል፡፡

ስኳር ኮርፖሬሽን በተለይ ከመልሶ ማቋቋምና ከስራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ልጆች ስራ የሚያገኙበት ሁኔታ በተለይ ፕሮጀክቱ ወደ ምርት ሲገባ ዕድሉ እንደሚፈጠር ተነጋግረናል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ስራ እስከሚጀምር አርሶ አደሮች የመስኖ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ወይም በመስኖ የለማ መሬት እንዲያቀርብላቸው አልያም በማህበር አደራጅቶ የሸንኮራ አገዳ ለፕሮጀክቱ የሚያቀርቡበትን ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት መነጋገራቸውን ተናግረዋል፡፡

የመፍትሄ ሃሳቡ ከቀረበ ሶስት ሳምንት ያለፈው መሆኑን እና ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት ክልሉ ይህን ያህል ችግር መኖሩን እንደማያውቁ፤ ችግሩን ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን እንደነገሯቸው አመልክተዋል፡፡ ከኮርፖሬሽኑ ጋርም እየተነጋገሩ መሆኑን በማመልከት መፍትሄ ካልተገኘ በአዋጁ መሰረት የሚመለከታቸው አካላት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ የአርጆ ዴዴሳ ግድቡ በስኳር ኮርፖሬሽን የተጀመረ መሆኑን በማስታወስ፤ እነርሱ ቢረከቡትም ቀድሞ ካለመሰራቱም ባሻገር በኋላም መልሶ በማቋቋም በኩል ያለውን ክፍተት እንደሚቀበሉት ይናገራሉ፡፡ 373 አርሶ አደሮች ተነሱ በተባለበት አካባቢ 80 ሺ ሄክታር ለማልማት 50ሺ ለስኳር ፕሮጀክቱ ፣30 ሺ ደግሞ ለአካባቢው ህብረተሰብ የመስኖ ልማት የታሰበ ቢሆንም በቅንጅት የመስራት ክፍተት አለ ይላል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አሸናፊ ካሳ በበኩላቸው፤ አንዳንድ እርምጃዎችን ለመውሰድ ተሞክሯል፡፡የተገባው ትልቅ ግድብ ሳይሆን አነስተኛ ግድብ ነው፡፡የተኛው ውሃ የጎዳቸውን ሰዎች ለመታደግ እና እስከ ክረምት በዛው ቦታ እንዳይቆዩ ይሰራል፡፡ ለተፈናቃዮች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ካሳ ይከፍላል፡፡ ነገር ግን ቀድሞ መሰራት ነበረበት የሚለው እንደሚያስማማ ተናግረዋል፡፡

ይህ ማለት ግን እስከአሁን ምንም አልተሰራም ማለት ሳይሆን፤ የሚቀርቡ የካሳ ጥያቄዎች ምላሽ ሲያገኙ እንደነበር፣ለአብነት በሊሙ ሳቃ ወረዳ ለ698 አርሶ አደሮች የቀረበው የ112 ሚሊዮን ብር የካሳ ጥያቄ ተስተናግዶ ገንዘቡ ለወረዳው ተልኳል፡፡ ወረዳውም 60 ሚሊዮን ብሩን አከፋፍሏል፡፡ የመሰረተ ልማት ስራዎችም ተጀምረዋል፡፡

በቦርቻ ወረዳም ለ634 አርሶ አደሮች 88 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ተጠይቆ 75 ሚሊዮን ብር ተከፍሏል፡፡ ነገር ግን አሁንም ችግር መኖሩ አይካድም፡፡ ከክልልም ሆነ ከዞን እንዲሁም ከወረዳ እና በአጠቃላይ ከሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አያጠያይቅም፡፡ ያለበለዚያ ትልቁ ግድብ ሲገነባ አደጋው የከፋ ሊሆን እንደሚችልም ነው የሚያመላክቱት፡፡

ስኳር ኮርፖሬሽን

የስኳር ኮርፖሬሽን የካሳ እና የመልሶ ማቋቋም ተወካይ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ደረሰ ለገሰ በበኩላቸው፤ ለማህበረሰቡ ካሳ የመስጠትና የማቋቋም ስራ ከገንዘብ እጥረትም ሆነ ከሌላ ችግር ጋር ተያይዞ ክፍተት ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም እየተሰራ ነው፡፡ በደሌ ወረዳ ላይ 12 ሚሊዮን ብር የካሳ ጥያቄ ቀርቦ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በትርጉም ስህተት ዘግይቷል፡፡ በቀሪው ጊዜ ግን ይለቀቃል፡፡

አርጆ ዴዴሳም ሆነ ጣና በለስ የስኳር ፕሮጀክቶች የአካባቢውን ህዝብ ከመጉዳት ይልቅ ጠቃሚ መሆን አለባቸው የሚለው አስተያየት ትክክል መሆኑን በመግለፅ፤ ምንም እንኳ በቂ ባይሆንም በግንባታ ሂደት ከፍተኛ ሙያ የሚጠይቁትን ካልሆነ በስተቀር ሌላው በአካባቢው ህዝብ እንደሚሰራ እና የስራ ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን ፣ልማቱ ሲቀጥልና ወደ ምርት ሲገባ የስራ ዕድሉ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ይገልፃሉ፡፡

     ተጠያቂው ማን ነው?

የኦሮሚያ ክልል የህዝብ እንባ ጠባቂ ቀሲስ በላይ መኮንን በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ አስፈላጊ እና አገርን የሚጠቅም ቢሆንም በልማቱ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ተጎድተዋል፡፡ በግዴለሽነት የሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ ብዙዎች በድንኳን እየኖሩ ነው፡፡ የስኳር ኮርፖሬሽኑም ሆነ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ ክልሉም ሆነ ወረዳው ባጠፉት ጥፋት ህዝብ ተጎድቷል፡፡ የችግሩን ባለቤት ወደ ሌላ መወርወር አያዋጣም፡፡ በፍጥነት መፈታት ያለበትን ችግር በአስቸኳይ መፍታት ይገባል፡፡ ሁሉም ግዴታውን መወጣት አለበት፡፡ የኦሮሚያ ክልል የደረሰውን ሪፖርት ተከትሎ በማግስቱ ኮሚቴ አቋቁሞ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን አሳውቋል፡፡ ልክ እንደዚህ ፈጣን እንቅስቃሴ ማድረግና ችግሩን መፍታት ካልተቻለ ህዝቡም ፕሮጀክቱን ይቀበለዋል ለማለት ያዳግታል፡፡

እንደተባለው የቅንጅትና ያለመናበብ ብቻ ሳይሆን በጥብቅ ሥነሥርዓት ያለመመራት ክፍተት በመኖሩ ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች ከተፈናቀሉ በኋላ የሚሰጥ ካሳ ለዓመት ከዘገየ የብሩ ዋጋ ምን ያህል እንደሚቀንስ ማሰብ ይገባል፡፡ ጊዜው ተወስኖ ችግሩ የሚፈታበት፤ ምትክ ቦታውም ሆነ ካሳው የሚሰጥበት ሁኔታ በግልፅ መቀመጥ እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡    

 የህዝብ እንባ ጠባቂ ዋና እንባ ጠባቂዋ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቶቹ አገርን የሚጠቅሙና የህብረተሰብን የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽሉ ቢሆኑም፤ ህዝብን ካፈናቀሉ ልማት ናቸው አይባሉም፡፡ 373 አባወራዎችን ለአንድ ዓመት ከስምንት ወር በመጠለያ ያስቆየ የልማት ስራ የአካባቢውን ህብረተሰብ የሚጠቅም ነው ለማለት ያዳግታል፡፡

የክልልም ሆነ የፌዴራል ተቋማት የምርምር ግኝቱን ያምናሉ፡፡ ችግሩን ይፈታ ሲባል ደግሞ፤ ችግሩን ከማወቅ አልፈው ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ተቋማቱ ‹‹ይህ የኔ ሥራ አይደለም›› ካሉ እንደመርህ የሚወሰደው በልማቱ ስራ ህዝብን የማሳተፍ ሂደት ይስተጓጎላል፡፡ ህዝብ ቀድሞ ተወያይቶና ተሳትፎ ቢሆን መዘግየት ቢኖርም ቢያንስ ማፈናቀሉ ይቀር ነበር፡፡ አሁንም ያለምንም ተጨማሪ ጊዜ በድንኳን ያሉና የተፈናቀሉትን አርሶ አደሮች ችግር መፍታት ያስፈልጋል፡፡

ክረምት ሳይመጣ መኖሪያ እናበጅላቸዋለን የሚለው ሃሳብ በደንብ መታየት አለበት፡፡ ከአራት ወር በፊት 33 ህፃናት ህይወታቸው ካለፈ በቀጣይ ካለፉት አራት ወራት ተጨማሪ አራት ወራት እንዲቆዩ ማሰብ ምንም እንኳ የዝግጅት ጊዜ ቢያስፈልግም ከባድ ነው፡፡ ቢያንስ ባሉበት ሁኔታ በደህንነት እንዲኖሩ ተገቢው ድጋፍ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ነው ያመለከቱት፡፡ የመፍትሄ ጊዜው ከራቀ ተጎጂዎቹን ጭራሽ ማግኘት እንደማይቻልም ነው የሚያሳስቡት፡፡

የፕሮጀክቶቹ መገንባት ወሳኝነቱ ባይካድም ባለመቀናጀትና በአግባቡ ባለመሰራቱ በሚጎዱ ሰዎች፤ ልማቱ ላይ ዕምነት እንዳይኖራቸውና እንዳይቀበሉት ያደርጋቸዋል፡፡ የወረዳ ሃላፊዎች መቀያየርና ሌሎችም የሚነሱ ምክንያቶች አጥጋቢ አለመሆናቸውን በመጠቆም፤ ሰነድ አዘጋጅቶ ማንም ቢመጣ ሊሰራው በሚችል መልኩ ማስቀመጥና ሃላፊነትን መውሰድ ተገቢ መሆኑንም ነው ዋና እንባ ጠባቂዋ የተናገሩት፡፡ 

ማጠቃለያ

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ስኳር ኮርፖሬሽን፣የሁለቱም ክልሎች በየደረጃው ያለ የስራ ኃላፊዎች የአርሶ አደሮቹን ችግር በመፍታት ረገድ የእስካሁኑ ጥረታቸው ተገቢ ነበር ማለት አይቻልም።ምክንያቱም የህዝብ እንባ ጠባቂ ምርምራ ሪፖርት ከደረሳቸው በኋላ እንኳን ፈጣን ምላሽ  ሰጥተዋል ማለት አይቻልም። ፋብሪካው የሚሰራው ለሰው ተብሎ ነው።ለሰው ተብሎ ግን የሰውን ውድ ህይወት አደጋ ላይ መጣል የለበትም።ስለዚህ ይህ ለስኳር ተብሎ የተከፈለ ውድ ዋጋ መቆም አለበት።የሰው ህይወት በገንዘብ አይተመንም።ስለዚህ ፈጣን ምላሽ-ውድ የሆነውን የሰው ህይወት ከአደጋ ለመታደግ። 

 

ምህረት ሞገስ

Published in ፖለቲካ

በዓለም በኢኮኖሚያቸው በቀዳሚነት ላይ የሚገኙ ቻይናና አሜሪካ በውጭ ንግድ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም በኢንዱስትሪ ምርታማነት ተመጋጋቢ ሆነው መቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በሚከተሉት« አሜሪካ ትቅደም» መርሃቸው ለሁለቱም አገራት የማይበጅ መሆኑ አንድ አንድ ምሁራን ይናገራሉ፡፡

ቻይና ግዙፍ የሚባሉ አምራች ፋብሪካዎቿ በአሜሪካ በጥሩ ትርፍ የሚንቀሳቀሱ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህም ቻይናውያን ኢንቨስተሮች በአገራቸው አምርተው ወደ አሜሪካ ያለቀለት ምርት ከማቅረብ ይልቅ በአሜሪካ አምርተው ለተለያዩ ገበያዎች የሚቀርቡት ምርት በጣም ትርፋማ መሆኑ ይገልጻሉ፡፡ ምክንያቱም በቻይና ከፍተኛ ግብር የሚጣልባቸው ሲሆን በአሜሪካ ግን በአንጻራዊ በጣም ዝቅተኛ ግብር ይከፍላሉ፡፡

የአሜሪካው አዲሱ ፕሬዚዳንት በአሜሪካን ኩባንያዎች ላይ የተጋረጡ ችግሮችን በሚጠቅ ሱበት ጊዜ በዋናነት ያስቀመጡት ችግር ከፍተኛ የሆነ የግብር ክፍያ እና በጣም በዝቅተኛ ዋጋ በአሜሪካ ገበያ ውስጥ የውጭ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ማቅረባቸው መሆኑን አመልክ ተዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱ አነጋገር በግልጽ የሚያሳየው ቻይና የፋብሪካዎቻቸው መዳከም ቀዳሚ ተዋናይ መሆንዋ ነው፡፡ በርግጥም የቻይና ባለሃብቶች በአገራቸው አምርተው ከሚያገኙት ትርፍ ይልቅ በአሜሪካ አምርተው የሚያተርፉት ትርፍ በእጅጉ የላቀ መሆኑ በአሜሪካ በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች ይናገራሉ፡፡

እንደሚታወቀው በኤሽያ አገራት በብዛት የሚመረቱና በስፋት በርካሽ ዋጋ የሚሸጡ ምርቶች በቻይና የተሰራ ወይም «Made in China» የሚል መለያ ምልክት አላቸው። መለያ ምልክቱም ለዘመናት በስፋት ለገበያ ከሚቀርቡ ምርቶች ጋር የተለመደ ነው፡፡ የፕሬዚዳንት ትራምፕ በቻይና ላይ ያላቸው አቋም  ላይ ግን የአገራቸው ፋብሪካዎች የማምረት ስራዎቻቸውን እየተገበሩ ቢሆንም  በኢንዱስትሪ የዓለም መሪነታቸው ግን በቻይና የበላይነት የተወሰደ መሆኑን ነው፡፡

የቻይና ፋብሪካዎች በሌሎች አገራት በዝቅተኛ ዋጋ በሚመረቱ ምርቶች ከጨዋታ ውጭ በመደረጋቸው ብቻ ሳይሆን ፋብሪካዎቹ በአገራቸው ወደ ኋላ የሚጎትት ችግር ስለተጋረጠባቸውም ነው፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ የግብር ክፍያ ሲሆን በአሜሪካ ከሚጣልባቸው ግብር በላይ የቻይናው  ከ35 በመቶ በላይ ብልጫ አለው ሲሉ ቻይናዊው የመኪና መስተዋት አምራች ኩባንያ ፉዮው መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ቾ ታክ ባለፈው ታህሳስ ወር ተናግረው ነበር፡፡

በቻይና በተለይ የግብር ስርዓቱ በርካቶችን ያላስደሰተ በመሆኑ የቻይና ፋብሪካዎች በአገራቸው ጤነኛ የማምረት ስራቸውን ለማከናወን ይከብዳቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት እንደነ ቾ ታክ የመሳሰሉ ባለሃብቶች በአገራቸው ከማምረት ይልቅ በአሜሪካ በማምረትና በመሸጥ ነው ትርፋማ የሚሆኑት፡፡ባለ ሃብቱ እአአ ከ2014 ጀምሮ በአሜሪካ እስከ 750 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርገዋል፡፡

በተመሳሳይ በአሜሪካን አገር ምርታቸውን እንዲያመርቱ ቻይናውያን ባለሃብቶች ከሚበረ ታቱባቸው ምክንያቶች ነጻ የመሬት አቅርቦት፣ ከቻይና በግማሽ ያነሰ የኤሌክትሪክ ክፍያ እንዲሁም የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ በአንድ አምስተኛ ስለሚቀርብላቸው መሆኑን ቾ ያብራራሉ፡፡ በአሜሪካ አምርቶ ወደ ገበያ ከማቅረብና በቻይና አገር አምርቶ ከማቅረብ ያለው ልዩነት ሲታይም ትርፉ በአሜሪካ አምርቶ በማቅረብ የሚገኘው ከ10 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለው ነው፡፡

 በተጨማሪ እሴት ታክስ ሲታይ አሜሪካ ታክስ ወይም ግብር የምትጥልለው በኩባንያው ገቢ ብቻ ሲሆን ቻይና ግን በገቢም በእያንዳንዱ የምርቱ በገበያ ስርጭቱ ላይ ግብር ትጥላለች፡፡ ይህ ማለት አንድ እቃ በጥሬ እቃው ሲገዛ፣ ሲመረት፣ ሲሸጥ እንዲሁም ከነጋዴም ዳግም ሲሸጥ ግብር እንደሚከፈልበት ነው፡፡ በኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃ ወደ አለቀለት ምርት የሚለውጡ 17 በመቶ ተጨማሪ እሴት ታክስ በቻይና ይከፍላሉ፡፡

እንደ ቾ የመሳሰሉ ባለሃብቶች በአገራቸው ቻይና እንዳያመርቱ የግብር እንቅፋት ስለሚሆ ንባቸው በተደጋጋሚ በሚያሰሙት ቅሬታ ተከትሎ የቻይና መንግስት እአአ በ2011 የግብር ማሻሻያ ፕሮግራም ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ዓላማውም ቀስ በቀስ የቢዝነስ ግብር በገቢ ላይ ለማስቀረት ሲሆን ይህ አዲስ የግብር አሰራር መንግስት ባለፈው ዓመት ከግንቦት እስከ ሕዳር ከኢንዱስትሪዎች ማግኘት የሚገባው 17 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ አሳጥቶታል ሲሉ የአገሪቱ የፋይናንስ ሚኒስትር ዢዋ ጄይ ተናግረዋል፡፡  በአዲሱ የግብር አከፋፈል ስርዓትም 1 ነጥብ 5 በመቶ ግብር ከፋዮች ብቻ ናቸው የግብር ጭማሪ የተገኘባቸው፡፡

ይሁን እንጂ አምራቾች በቀዝቃዛው ኢኮኖሚ ትርፍን ማሰባሰብ እጅግ ስለሚከብዳቸው ይህን የግብር አከፋፈል ስርዓት የመቋቋም ፍላጎታቸው ቀንሷል። እንዲሁም ለዝቅተኛው ትርፍም ቢሆን የግብር ክፍያ ማስቀረትም ሊያሻሽለው እንደማይችል ቻይናዊው የኢኮኖሚ ምሁር ባ ሃይዪንግ ይናገራሉ፡፡

የቢዝነስ ታክስን በአግባቡ የመሸፈን አቅም ከመጠን በላይ የምርት አቅርቦት ምክንያት በገበያ የመጨናነቅ፣ ከፍተኛ የጉልበት ዋጋ፣ዝቅተኛ ተጨማሪ እሴትና በገበያ የተመናመነ ትርፍ እንዲሁም በአምራች ኢንዱስሪዎች የሮቦት ቴክኖሎጂካዊ ምጥቀት የመጠቀም  ምክንያቶች ባለሃብቱ እንዲዳከም አድርጎታል ሲሉ የባ ሃይዪንግ አጋር እና ተቀማጭነቱ በቤጂንግ ያደረገ የታወቀ የታክስ ኤጀንት ኩባንያ ዦንግሁይ ነው፡፡

በቻይና መንግስት የተደረገ መጠነኛው የታክስ ማስተካከያ በትራምፕና ሪፐብሊካኑ በሚመሩት ካቢኔ ከቀረበው ሲነጻጸር ከፍተኛ ልዩነት አለው፡፡ ተመራጩ ፕሬዚዳንት የኮርፖሬት ታክስ ወደ 15 በመቶ ዝቅ እንዲል ያቀዱ ሲሆን የሪፐብሊካኑ ካቢኔዎችም ከዚህ በላይ ዝቅ እንዲል ይሞግታሉ፡፡ ይህም ካለው የ30 በመቶ ታክስ ወደ ዜሮ አካባቢ ዝቅ እንዲል የቀረበው የካቢኔው ምክረ ሃሳብ አሜሪካን ኢንቨስት ለማድረግ ይበልጥ የታክስ ማበረታቻ ያላት ያደገች አገር ያደርጋታል ይላሉ በቦስተን ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ላውረንስ ኮትሊኮፍ፡፡

በአሜሪካና ቻይና የሚደረጉ በርካታ ውስንነቶች ቻይናውያን አምራቾችን ቁጣ የሚቀሰቀስ ነው፡፡ ለእነ ፉዮውና መሰል የቻይና ፋብሪካዎች በአሜሪካ በይበልጥ ትርፋማ ያስደረጋቸው ምክንያት በአካባቢው መንግስታት የሚደረግላቸው ማበረታቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ፋብሪካው በኦህዮ የ30 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ የጥቅማጥቅም ፓኬጅ የተበረከተለት ሲሆን በስፍራው በ15ሚሊዮን ዶላር የገዛው 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ጫማ ስፋት እና ሌላው ለግንባታ ያወጣው 15 ሚሊዮን ዶላር ለመሸፈን እንደረ ዳው ቾ ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ፋብሪካዎቹ 1ሺ700 የሚሆኑ የስራ እድሎች በአሜሪካ ፈጥሯል፡፡

በሚቀጥለው ግን እነ ፉዮውና ሌሎች ፋብሪዎች በአሜሪካ ፋብሪካ እንዲገነቡ ከቻይና መንግስት ተቆጣጣሪ አካል የንግድና ብሔራዊ ልማትና ማሻሻያ ኮሚሽን ጨምሮ እውቅና ካልተሰጣቸው በስተቀር አይችሉም፡፡ የቻይና መሪዎች አንድ አንድ ፋብሪካዎቻቸው በውጭ አገራት በመዞር የሚያደርጉት የማምረት ተግባር ለእንደ ትራምፕ «አሜሪካ ትቅደም» አቋም  የሚኖረውን ፋይዳ ታሳቢ ያደርጋሉ፡፡ በዚህም የቻይና መንግስት ፖሊሲ እንደ ፉዮው የመሳሰሉ ፋብሪካዎች በውጭ አገራት ከሌሎች የውጭ ድርጅቶች እንደነ ጀነራል ሞተርስ በመሰሉ መልካም ትብብር በመመስረት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያበረታታ ነው ይላሉ የኢኮኖሚ ሙሁሩ ባ ሃይዪንግ፡፡ ጀነራል ሞተርስ ፉዮው የመስተዋት አምራች የመሸጫ ዋጋ ለመቀነስ የማምረቻ ፋብሪካው በአሜሪካ በስፋት እንዲንቀሳቀስ ድጋፉን ሰጥቷል፡፡

ይህ የቻይና ኩባንያዎች በአሜሪካ የስራ ዕድል የመፍጠራቸው አንድ ማሳያ ቢሆንም ሚስተር ትራምፕ በቻይና ላይ ያስቀመጡት ቀጭን እርምጃ የማይመሳሰል እንደሆነ ምንም እንኳ የኢኮኖሚ ሙሁራን ዝቅተኛ የጉልበት ዋጋ በማንም አገር ላይ መኖር በአሜሪካ የኢንዱስትሪ ስራ መቀዛቀዝ ያመጣል ማለቱ ተገቢ ባይሆንም፡፡

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት አሜሪካ እአአ ከ2000 እስከ 2006 የማኑፋክቸሪንግ ስራዎች የ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎቿ ከስራ መቀነሱን አሳይቷል፡፡ ይህ ግን 13 በመቶ ብቻ በዓለም አቀፍ ንግድ ምክንያት ያስከተለው ሲሆን 85 በመቶ ደግሞ በቴክኖሎጂ እድገት ማለት በኮምፒውተራይዜሽን ያስከተለው መሆኑ ፋይናንሻል ታይምስ ጠቁሞ ነበር፡፡

እነዚህ እውነታዎችና የቻይና ኢንቨስትመ ንቶች በአሜሪካ የትራምፕ አቋም ማለትም ቻይና የአሜሪካ የስራ ዕድልና ምንዛሬ ወስዳዋለች ብሎ መክሰስ ከጅምሩ በሁለቱም የዓለም የኢኮኖሚ ታላላቅ አገሮች መካከል ያለው የንግድ ጦርነት ሊቀየር አይችልም፡፡ ለጊዜው ለአሜሪካ ፋይዳ ያለው መስሎ ቢታይም ሁለቱም አገራት መጨረሻ ላይ ግን ተጎጂ መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ የቦስተን ዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት የትራምፕ ግለኝነት ከቻይና ጋር የንግድ ጦርነት የመጀመር ውሳኔና የአሜሪካን ምንዛሬ ቻይና ጠራርገዋለች ብሎ መክሰስ አንድ የኢኮኖሚ እውቀት ከሌለው ሰው የሚፈጠር ትልቅ ስህተት ነው ይላሉ፡፡  ዘገባው የግሎባል ሪሰርች ድረገጽ ነው፡፡.

 

በሪሁ ፍትዊ

Published in ዓለም አቀፍ

ከሰባት አስርት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ መሬት 40 ከመቶ ገደማ በደን የተሸፈነ እንደነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ። የዛሬ አርባ ዓመት ግን ይህ ሽፋን ከ10 በመቶ በታች ወረደ። በ70ዎቹ መጀመሪያ ላይ ደግሞ 4 በመቶ ያህል ብቻ ነበር። በየአካባቢው ካሉ አዛውንቶች የሚገኙ መረጃዎችም የዚህን 40 በመቶ የነበረው ደን በዚህ ደረጃ የማሽቆልቆሉን ትክክለኛነት ያመለክታሉ። በአርባዎቹና በሃምሳዎቹ እድሜ ክልል ያለነው ኢትዮጵያውያንም ቢሆን፤ በተለይ ገጠር ያደግነው በእጽዋት ተሸፍኖ የነበረው መሬት እጅግ መሳሳቱን መመስከር እንችላለን።

እኔ በግሌ ከሰላሳ አምስት ዓመታት በፊት ልጅነቴን ያሳለፍኩበትን የማወቀውን አካባቢ ከሁለት ዓመት በፊት የማየት አጋጣሚ አግኝቼ ያየሁትን ለማመን ተቸግሬያለሁ። በእንጆሪ፣ በአጋምና በመሰል ተክሎች ተሸፍኖ የነበረውና ከብቶች የሚሰማሩበት ሰፊ መሬት የድሮውን ምልክቱን አንድም ሳይተው የእርሻ ማሳ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በቁጥቋጦው ይጠለሉ የነበሩትን የተለያየ ዝርያ ያላቸው ጥንቸሎችና መሰል አነስተኛ እንስሳት አሁን በአካባቢው የሚኖሩ ህጻናት አያውቋቸውም። ወደ መንደር እየዘለቁ፤ አንዳንዴም በሰብል ላይ ጉዳት ያደርሱ የነበሩ ከርከሮዎች አሁን የሉም። በበጋ ለአካባቢው እንግዳ የሆነ ሰው መልካ ተፈልጎለት ልብሱን ሰብስቦ ይሻገረው የነበረው ወንዝ ህጻናት ዘልለው የሚሻገሩት ትንሽ ጅረት ሆኗል። እርግጥ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ የአካባቢው ህዝብ ቁጥር በሶስት እጥፍ ገደማ አድጓል። ድሮ በቁጥቋጦ ተሸፍኖ የነበረው ቦታ አሁን የእርሻ ማሳ ሆኗል። ይህን መሬት ወደእርሻ ማሳነት የቀየረው አዲሱ ትውልድ ነው።

ይህ የእኔ ተሞክሮ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ያለውን እውነታ ያንጸባርቃል። በ2003 ዓ.ም በተለይ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን፤ እንዲሁም በትግራይ ክልል የተለያዩ ዞኖች የተሰሩ የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤና የተፋሰስ ልማት ስራዎችን የመጎብኘት እድል አግኝቼ ነበር። በዚህ ጉብኝት የታዘብኩት ነገር ይህን የሚያረጋግጥ ነው። በእነዚህ የአማራና የትግራይ አካባቢዎች የተፈጥሮ ሃብት ላይ የደረሰው ውድመት ረዘም ያለ እድሜ ያስቆጠረ ነው። እድሜያቸው በአርባዎቹ ክልል ያሉ ሰዎች እንኳን ስለአካባቢው የቀድሞ ገጽታ  የሚያውቁት ነገር ምንም የለም። ትውስታ ያላቸው አዛውንቶች ናቸው።

 በተፈጥሮ አካባቢዎቹ ላይ ጉዳት መድረስ ከጀመረ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ አስቆጥሯል። የአካባቢዎቹን የቀድሞ ገጽታ የሚያመለክቱ ማስረጃዎች ግን አሁንም አሉ። ዋነኞቹ የቤተክርስቲያን ግቢዎች ናቸው። የደከመው ሰው ቀትር ላይ የሚያርፍበት ዛፍ በሌለበት ምድረ በዳ የሚገኙ የቤተክርስቲያን ግቢዎችና ገዳማት ተለይተው አረንጓዴ ደሴት ሆነው ይታያሉ። እነዚህ የቤተክርስቲያን አጸዶች ድሮ አካባቢው በዛፍ የተሸፈነ እንደነበረ ብቻ አይደለም የሚመሰክሩት፤ በአካባቢው የነበሩት አገር በቀል ዛፎች ምን አይነት እንደነበሩም ያሳያሉ።

ከላይ በአጭሩ ያነሳሁት እውነታ የተፈጥሮ አካባቢያችን ላይ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ሁላችንም የየራሳችንን አካባቢ በማስታወስ እንድንገነዘብ ለመኮርኮር ያህል ነው። ይህ በተፈጥሮ ላይ የደረሰው ጉዳት አሁን በመንግስትና በህዝብ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። የወደመው ተፈጥሯዊ አካባቢ እንዲያገግም የተቀናጀ የአካባቢ ልማት/የተፋሰስ ልማት ስራ እየተከናወነ ይገኛል። በተለይ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ትልቅ ለውጥ ያመጣ የአካባቢ ልማትና እንክብካቤ ስራ ተከናውኗል። እነዚህ የአካባቢ ልማቶች እስከ 50 በመቶ ተዳፋት በሆኑ የተራቆቱ ተራራዎችና ኮረብታዎች ላይ እርከን በመስራት፣ ዛፍና ሳር በመትከል ላይ ያተኮረ ነው። ከዚህ በተጨማሪ፤ በራሳቸው ሊያገግሙ የሚችሉ አካባቢዎችን ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ በመከላከል ድንቅ ውጤት ተገኝቷል።

በዚህ ዙሪያ የተከናወኑና ሊከናወኑ በታቀዱ ተግባራት ላይ መረጃዎችን ከማቅረቤ በፊት በትግራይ ክልል አሁን መጠሪያውን በማላስታውሰው አካባቢ ከአርሶ አደሮች የሰማሁትን አንድ ነገር ላካፍላችሁ ወድጃለሁ። የአካባቢው የተፈጥሮ ሃብት ክፉኛ የተጎዳ እንደነበረ ሰምቻለሁ። በአካባቢው የሚገኝ ተራራ ያገጠጠ ድንጋይ እንደነበረ፣ በአካባቢው ፊጪጭ የሚል ውሃ እንዳልነበረ አርሶ አደሮቹ አጫውተውኛል። እኔ በተመለከትኩበት ወቅት ግን ከጉዳቱ ይልቅ በማገገም ላይ ያለ መሆኑ ነው ጎልቶ የሚታየው። በተራራው ላይ የተለያዩ የተፋሰስ እንክብካቤ ስትራክቸሮች ተገንብተዋል። የድንጋይ እርከኖች፤ የተለያየ ቅርጽ፣ ስፋትና ጥልቀት ያላቸው የውሃ መከተሪያ ጉድጓዶች ወዘተ... በተራራው ላይ ይታያሉ። ጋራው በሰምበሌጥ ሳር ተሸፍኗል። ቁጥቋጦዎች ወርሰውታል። ገና እድገታቸውን የጀመሩ የተለያየ ዝርያ ያላቸው ዛፎች እዚህም እዚያም ይታያሉ።

ይህ ብቻ አይደለም፤ የአካባቢው ሰዎች አይተዋቸው የማያውቋቸው ምንጮች ከተራራው ስር ኩልል ያለ ውሃ ያፈስሳሉ። ከተራራው ስር መንጭተው የሚፈሱት ወንዞች ሰፊ ጉድጓድ ተቆፍሮላቸው ተገድበዋል። ወቅቱ በጋ ቢሆንም ምንጩ የሚፈስበት አካባቢ ለምለም አረንጓዴ ነው። ምንጮቹ የተገደቡበት አካባቢ በመስኖ የለሙ የበቆሎና የተለያዩ የአትክልት ማሳዎች ይታያሉ። ከብቶች ከየአካባቢው መጥተው ከተከተረው ሰፊ ጉድጓድ ውሃ ይጠጣሉ። የአካባቢው ነዋሪዎች ድሮ አንድ ዘለላ ነዶ የማይታይበት ጋራ ያበቀለውን ከሰው ቁመት የሚረዝም ሳር እያጨዱ ከብቶቻቸውን ይመግባሉ።

ታዲያ ይህን በጉልህ የሚታይ ለውጥ ያመጣ ስራ ለማከናወን ምን እንዳነሳሳቸው የአካባቢውን አርሶ አደሮች ጠየኳቸው። ሳይዋሹ ነገሩኝ። እኛ በራሳችን አልተነሳሳንም ነበር ያሉኝ፤ ወደአንድ ወጣት የግብርና ባለሙያ እያመለከቱኝ፤ እርሱ ነው ዘወትር እየመጣ እየሰበሰበ፣ እያስተማረ፣ እየመከረ ለስራ እንድንወጣ ያደረገን አሉኝ። ታዲያ መጀመሪያ ባለሙያውን ጠላነው። መጥላት ብቻ አይደለም፤ ረግመነዋልም። እየረገምነው የጀመርነው ስራ አሁን ውጤት አስገኝቷል። እናም የስራችንን ውጤት ማየት ስንጀምር፣ ባለማወቃችን ባደረግነው ተጸጽተን ባለሙያውን መልሰን መረቅነው። አሁን እየመረቅነው ነው አሉኝ። እርግማንን ወደ ምርቃት የለወጠ ድንቅ ተግባር፣ ድንቅ ውጤት!

በዚህ በጠቀስኩት አካባቢ የተገኘው ውጤት ባለፉት አስር ዓመታት በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች የታየ ነው። በአካበቢ ልማትና እንክብካቤ የተከናወነው ተግባር በየአካባቢው የውሃ ምንጮችን አስገኝቷል። ደርቀው የነበሩ ጅረቶች ዓመቱን ሙሉ እንዲፈሱ፣ መጠናቸው ቀንሶ የነበሩ ወንዞች እንዲጨምር አድርጓል። በየአካባቢው አነስተኛ የመስኖ እርሻ ማከናወን ተችሏል። የመጠጥ ውሃ፤ የከብቶች መኖና ውሃ በቅርብ ማግኘት አስችሏል። በብዙ አካባቢዎች ባለፈው ዓመት ተከስቶ የነበረውን ድርቅ በመጠኑ መከላከል የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ማገዙንም መረጃዎች ያመለክታሉ። ምንም ጥቅም የማይሰጡ የነበሩ ተዳፋት አካባቢዎች መልማታቸው ለገጠር ስራ አጥ ወጣቶች የስራ እድል የፈጠረ ተጨማሪ ሊለማ የሚችል መሬት አስገኝቷል። በርካታ ወጣቶች ተደራጅተው በተዳፋት አካባቢ የበቀለን ሳር ለከብት መኖነት በመጠቀም የከብት ማደለብና ርባታ ስራ ላይ መሰማራት ችለዋል። ወደለምነት የተቀየረው አካባቢ በርካታ ወጣቶችን በንብ ማነብ ስራ ላይ ማሰማራት አስችሏቸዋል።

የተፋሰስ ልማት ስራ ዘላቂ ፋይዳም አለው። በየአካባቢው ለተለያየ ዓላማ የሚገነቡ ግድቦችን፤ በተለይ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከደለል በመከላከል የተገነቡበትን ዓላማ በአግባቡ ማከናወን እንዲያስችሉ፤ የፕሮጀክት እድሜያቸውን ሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ያስችላሉ። በተለይ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጀመር በኋላ በአባይ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮች የሚያከናውኑት የተፋሰስ ልማት ግድቡን ከደለል የመከላከል ግብ ያለው መሆኑን ማወቃቸው ከፍተኛ ተነሳሽነት እንደፈጠረባቸው ይታወቃል። ይህ ተግባራቸው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዳበረከቱት አስተዋጽኦም ተቆጥሮላቸዋል።

ያም ሆነ ይህ፤ የተፋሰስ ልማትና የአካባቢ እንክብካቤ ስራ አሁንም ቀጥሏል። በያዝነው ወር በአምስት ክልሎች (በትግራይ፤ በአማራ፤ በኦሮሚያ፤ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ) የ2009 ዓ.ም የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ በይፋ ተጀምሯል። በዘንድሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ላይ ከ24 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዝግጅት ምእራፉ በእነዚህ ክልሎች ለሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ 6 ሺህ 706 ተፋሰሶችን ለማልማት መታቀዱን የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታውቋል። ከ15 ሚሊዮን በላይ ለስራው የሚያስፈልጉ የእጅ መሳሪያዎችም መዘጋጀታቸውን፣ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮችና ባለሙያዎች፤ እንዲሁም ቀያሽ አርሶ አደሮች በተፋሰስ ልማት ዙሪያ አስፈላጊውን ስልጠና እንዲያገኙ መደረጋቸውንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የተፈጥሮ ሃብት ልማትና እንክብካቤ ስራው ዓላማ ባለፉት አስር ዓመታት ሲከናወን እንደነበረው ሁሉ፣ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክንያት የተጎዳ መሬት እንዲያገግም በማድረግ መሬቱ የሚሰጠውን ጠቀሜታ ማሳደግ ነው። የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራው የተራቆተውን መሬት ከንክኪ ነፃ ማድረግ፣ እርከን መስራት እና እፅዋት በመትከል በስነ ህይወታዊ መንገድ የተራቆተ መሬት መልሶ እንዲያገግም ማስቻልን ያጠቃልላል።

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራው አገሪቱ የተሻለ እንድትለማ የሚያደርግና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው፣ በየጊዜው የሚካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ልማት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲጓዝ እና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እንዲያደርግ ማህበረሰብ አቀፉ ስራ በሳይንስና በምርምር መታገዝ አለበት።

እንግዲህ የአገራችን የተፈጥሮ ሃብት ባለፉት ሰባት አስርት ዓመታት ክፉኛ መጎዳቱ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያስማማል። ጉዳቱ ለሰውም ተርፏል።የአየር ንብረት መዛባት-ድርቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄዷል። በተፈጥሮ ሃብት መጎዳት ምንጮች፣ ጅረቶችና ወንዞች በመድረቃቸው የህዝቡ በተለይ የአርሶና አርብቶ አደሩ የድርቅን ተጽእኖ የመቋቋም አቅሙ እጅጉን የተዳከመበት ሁኔታ ተስተውሏል።

ባለፉት አስር ዓመታት በየዓመቱ በሃያ ሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ለበርካታ ቀናት በተፈጥሮ አካባቢ ልማትና እንክብካቤ ስራ ላይ ተሰማርተዋል። አሁንም ይህንኑ በማከናወን ላይ ናቸው። ይህ ስራ ነጭ ላብ ጠብ እስኪል የሚከናወን አድካሚ መሆኑ ይታወቃል። ከተገኘው ውጤት አኳያ ሲታይ ግን ዘላቂ እፎይታ የሚያስገኝ ነው። ይህ የተፈጥሮ አካባቢ ልማት ስራ የተጣለበት አርሶ አደር ስራው አድካሚ ቢሆንም ዘላቂ እፎይታ የሚሰጥ መሆኑንና የውጤቱ ቀዳሚ ተጠቃሚም ራሱ መሆኑን ተገንዝቦ በወኔ ሊያከናውነው መነሳት አለበት። ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ሳይልፈሰፈሱ ከአርሶ አደሩ ጎን መቆም አለባቸው። ለዘላቂ እፎይታ ዛሬን እንድከም!

 

ኢብሳ ነመራ

Published in አጀንዳ
Sunday, 12 February 2017 19:44

ከፈረሱ ጋሪው አይቅደም!

ልማትን ማን ይጠላል? ማንም። ልማት ግን የሚወደደውና የሚደገፈው  የልማቱ ባለቤት ህዝብና ህዝብ ሲሆን ብቻ ነው። ህዝብ ያልተቀበለው ልማት ቢውል እንጂ አያመሽም፤ አያድርምም። ህዝብ ልማትን እንዲቀበለውና እንዲደግፈው ለማድረግ ደግሞ ቀላሉ መንገድ በፕሮጀክቶች ዙሪያ ከፈረሱ ጋሪው ያልቀደመ ተግባርን ማከናወን ነው።

እውነታው ይሄ ቢሆንም በኦሮሚያ ክልል የአርጆ ዴዴሳ እና በአማራ ክልል የጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ከፈረሱ ጋሪው ቀድሞባቸው ለአካባቢው ነዋሪ የልማት ቱሩፋት ከመሆን ይልቅ እርግማን እንደሆኑባቸው አዲስ ዘመን ያደረገው ማጣራት አረጋግጧል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ከመተግበራቸው በፊት ሊደረግ ይገባ የነበረው የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ባለመደረጉ ምክንያት ለልማት የታሰቡት ፕሮጀክቶች ለአካባቢው ህብረተሰብ የጥፋት በትር ሆነዋል።

የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በፕሮጀክቶቹ ዙሪያ ባደረገው የምርመራ ውጤት መሰረት፤ በኦሮሚያ ክልል የአርጆ ዴዴሳ የስኳር ፕሮጀክት እና ለፕሮጀክቱ  የሚያገለግለው የመስኖ ልማት ግድብ የአራት ወረዳ ሰዎችን ለጉዳት አጋልጧል፡፡ በዚህም ከ1000 የሚልቁ  አርሶ አደሮች ንብረታቸው በትክክል ሳይቆጠር፣ ካሳ ሳይከፈላቸው፣ ምትክ መሬትም ሳይሰጣቸው ከመኖሪያ ቤታቸው እንደዋዛ ተፈናቅለዋል፤ በላስቲክ መጠለያ እንዲኖሩ ተገደዋል፤ ለተላላፊ በሽታና ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፤ ከሁሉም የሚከፋው ደግሞ 33 ህፃናት በዚህ ችግር ሳቢያ ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡ ለግድብ ተብሎ የተሰራው ውሃ ሞልቶም 4 ሰዎችንና 64 የቤት እንስሳትን የአዞ ሲሳይ አድርጓል፡፡

በተመሳሳይ የአማራንና የቤንሻንጉል ክልልን አማክሎ የሚለማው የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክትም ተመሳሳይ ጉዳት ማድረሱን የተቋሙ ጥናት አረጋግጧል። ከሶስት ሺ በላይ አርሶ አደሮች የተለያዩ ጉዳቶች ደርሰውባቸዋል። ካሳ ያልተከፈላቸው፤ ምትክ እርሻ መሬት ያልተሰጣቸው፤ የተሰጣቸውም ቢሆኑ መሬቱ ምርታማ ያልሆነላቸው፤ ሌላም ሌላም ችገሮች ያሉባቸው አርሶ አደሮች ዛሬም ድረስ እያነቡ ናቸው።

እንባ ጠባቂም ይሄንን ጥናት አድርጎ ሲያበቃ፤ እርምት እንዲደረግ በክልልና በፌዴራል ደረጃ ቢያሳስብም እስካሁን ሁሉንም ቅሬታዎች የሚፈታ የማስተካከያ እርምጃ አልተወሰደም፤ ለጥፋቱ ተጠያቂው እኔ ነኝ የሚል አካልም አልተገኘም። ተቋሙም አሁንም ድረስ ጉዳዩ እልባት እዲያገኝ እያሳሰበ ይገኛል። ይህ ተቋም በተደጋጋሚ በአስፈጻሚው አካል የደረሱ የህዝብ በደሎችን እንዲያርም ለሚደረግለት የድረስልን ጥሪዎች ደብዳቤ ከመጻፍና ከማስፈራራት የዘለለ እርምጃ የማይወስድ በመሆኑ አስፈጻሚዎች ለተቋሙ ያላቸው ተገዥነት እየተሸረሸረ የመጣ ይመስላል። ያ ባይሆንማ ኖሮ ይህ ሁሉ በደል በግልጽ ባልተፈጸመ ነበር።   

በእንደዚህ አይነት ግልጽ በደሎች ምክንያት ህዝብ ቢያኮርፍና በልማቱ ላይ ጉዳት ቢፈጽም፤ ተጠያቂው ማን ሊሆን ነው?  በእርግጠኝነት የአካባቢው አስተዳደር የሚያወጣው መግለጫ ግን "ጸረ ልማት ኃይልች" የሚል እንደሆነ አያጠራጥርም። ለመሆኑ በዚህ እውነታ ላይ ጸረ ልማቱ ማነው? ህዝቡ? ወይንሰ አልሚው?። ህዝብ በየትኛውም መስፈርት ልማትን ሊቃወም አይችልም። ከአያት ቅድመ አያቶቹ የተላለፈለትን እርስት ሳይቀር ትቶ የሚነሳው እኮ ለልጆቹ የተሻለ ነገንና ልማትን ለማምጣት ካለው ጉጉት የተነሳ ነው። እውነታው ይሄ ከሆነ በልማት ስም እርስት አልባ  የሚያደርገው ልማት ለአርሶ አደሩ ምኑ ነው? ምንም። ስለሆነም የእነዚህ ፕሮጀክቶች ጠባሳ በአስቸኳይ ሊስተካከል ይገባል።

መንግስት በአንድ በኩል የህጻናት ሞት ቅነሳ የሚል መርሀ ግብር ነድፎና ከፍተኛ ባጀት መድቦ ይሰራል፤ በሌላው ጥግ ያለ የመንግስት አስፈጻሚ ደግሞ በልማት ስም ህጻናትን ለሞት ይዳርጋል። ይሄ እንዴት ይታረቃል? እንባ ጠባቂ ተቋምም እንደዚህ አይነት ግልጽ በደሎችን ካላስቆመና እንባም ካልጠረገ ምን ይሰራል? የማንንስ እንባ ሊያብስ የዴሞክራሲ ተቋም ተብሎ ተሞሽሮ ይቀመጣል?

አስፈጻሚው አካልም በአንድም በሌላም የሚፈጸሙ ስህተቶችን ማረም ከፈለገና ቁርጠኝነቱም ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት ከሆነ እንደ እንባ ጠባቂ ያሉ የገለልተኛ ተቋማትን ምከረ ሀሳቦችና የመፍትሄ እርምጃዎች አምኖ መቀበልና እርምት ማድረግ አለበት። በህዝብ ወንበር ላይ ተቀምጦ፤ በህዝብ በጀት እየተንቀሳቀሱም ህዝብን ማፈናቀል በየትኛውም አግባብ ልክ ሊሆን አይችልም። ስለሆነም ነገሩን "ሳይቃጠል በቅጠል" በሚል መርህ እልባት መስጠት ያስፈልጋል።

ለልማት መሬትን መልቀቅ ህገ መንግስታዊ ግዴታ ነው፤ ለተነሺ ካሳ መክፈልና ምትክ መስጠት ደግሞ ግዴታ። ስለዚህ አስፈጻሚው ህገ መንግስቱን ሲያስተገብር መብቱን ብቻ እየነጠለ ግዴታውን ወደጎን እየተወ ከሆነ፤ ጸረ ዴሞክራሲያዊና ኢ ህገ መንግስታዊ መሆኑን ማወቅ ይገባዋል።

በአርጆ ዴዴሳና በጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ዙሪያ ለደረሰው በደል ሁሉም አካል ተጠያቂ አይደለሁም ሲል ተከራክሯል። ከበደሉ ሁሉ የሚከፋው ደግሞ ይሄ ነው። ምክንያቱም በአንድም በሌላም ምክንያት የተፈጠረውን በደል ለማረም የተዘጋጀ አካል እንደሌለ ያሳያልና ነው። ስለሆነም መንግስት ለአርሶ አደሮቹ በደል ይድረስ፤ ያጠፋው አካልም ተለይቶ ይወቀስ፤ ይወገዝ። በልማት ስምም ከፈረሱ ጋሪው አይቅደም። 

Published in ርዕሰ አንቀፅ

የመኸር ዝናብ እጥረት ባስከተለው ድርቅ ለአምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዜጎች እርዳታ ማቅረብ መጀመሩን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንዳሉት፤ የመኸር ዝናብ እጥረት ባስከተለው ድርቅ በቆላማውና በአርብቶ አደር ቦታዎች፣ በሶማሌ፣ ኦሮሚያ ጉጂ፣ ቦረና ፣ ምእራብ ከፊል ባሌ እና በጉጂ ቆላማ ቦታዎች፣ ደቡብ ኦሞ በሰገን ህዝቦች አካባቢ በተከሰተው ድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ወገኖች እርዳታ እየተሰጠ ይገኛል።

በ2007 ዓ.ም እና 2008 ዓ.ም በድርቁ አስር ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ተጎጂዎች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ደበበ፤ በአሁኑ ወቅት ግን በዘጠኝ ዙሮች በተደረገው ዕርዳታ የተጎጂዎቹ ቁጥር ወደ አምስት ነጥብ ስድስት መውረዱን አመልክተዋል።

 በመኸር በተደረገው ጥናት  ለ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ህዝብ  የእለት እርዳታ የሚያስፈልገው በመሆኑ ለቆላማ አካባቢዎች ለኦሮሚያና ለሶማሌ ክልሎች እህል፣ ጥራጥሬና አልሚ ምግብ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ከእዚህ በተጨማሪ ለሶማሌ ክልል ከመደበኛው ውጪ 10 ሺ ኩንታል አልሚ ምግብ፣ አምስት ሺ ኩንታል ስንዴ ዱቄት፣ 15 ሺ እሽግ የዱቄት ወተት እንዲሁም 33 ኩንታል ሩዝ መሰጠቱን አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ደበበ ገለፃ፤ ለቦረና ቆላማ ስፍራዎች አራት ሺ 422 ኩንታል፣ ለጉጂ ዞን አምስት ሺ 97 ኩንታል፣ ለባሌ ቆላማ አካባቢ 24ሺ 700 ኩንታል፣ ለደቡብ ኦሞ አካባቢ 12ሺ 757 ኩንታል፣ ለሰገን ህዝቦች ሁለት ሺ 350 እንዲሁም  ለሶማሌ ክልል 64ሺ 920 ኩንታል  እህል ለተጎጂዎች ተሰጥቷል።

ድርቁ  እንስሳት ላይ ባስከተለው ጉዳት ሳቢያ ለተጎጂ አካባቢዎች ከ 200 ሺ በላይ እስር መኖ እንደተላከላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ በእንስሳት ሀብት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ በማሰብ በድርቁ የተጠቁት ስፍራዎች ላይ ልዩ ልዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ በዚህም በደቡብ ኦሞ ከፓርክ ሳር በማጨድ እንስሳቱን የመመገብ ስራ ሲሰራ፣ የሸንኮራ አገዳ ልማት ባለበት ቦታ ከስኳር ምርት የተረፈውን የሸንኮራ አገዳ ተረፈ ምርት ለእንስሳቱ መኖነት እንዲውል መደረጉን አቶ ደበበ ይገልፃሉ፡፡ በተጨማሪ ከአንድ ወር እስከ 45 ቀን የሚደርስ የእንስሳት መኖ ተከላ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያስረዳሉ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት እንዳስታወቀው፤ በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት በጋራ ለ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ህዝብ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎችን እያቀረቡ ነው። የመጠጥ ውሃ በቦቴ በማመላለስ፣ የእንስሳት መኖ አቅርቦት እና የህክምና አገልግሎትም ለድርቁ ተጠቂዎች እየተሰጠ ይገኛል። በድርቅ በተጠቁት አካባቢዎች የሚኖሩ የአርብቶ አደር ልጆች ከቀያቸው ሳይርቁ ትምህርታቸውን መቀጠል እንዲችሉም ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እየተደረገ ነው፡፡

 

ራጁ መሃመድ

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 3

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።