Items filtered by date: Monday, 13 February 2017

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት የትምህርት እንቅስቃሴ ውጤቶች የተመዘገቡበት ቢሆንም ጥራትን የማስጠበቅ ችግር ዋንኛ ፈተና መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም የትምህርትና ስልጠና ዘርፍ የመጀመሪያ 6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ወቅት እንደተናገሩት የትምህርት ጥራት ችግር አሁንም የክልሉ ዋነኛ ፈተና ሆኖ ዘልቋል። በመሆኑም በግብዓት አቅርቦት ፣በሂደትና ውጤቱ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ነው ብለዋል።
የተሟላ ሰብዕና ያለው ትውልድ ለመገንባት ትልቁ መሰረት የሚጣለው በትምህርት መሆኑን ጠቅሰው፤ የቅድመ መደበኛ ትምህርትን በጥራት ተደራሽ ለማድረግ የቅድሚያ ተሰጥቶት ርብርብ የሚደረግበት መሆኑን ገልጸዋል። የተማሪ ማቋረጥ እንዲሁም በገጠር ትምህርት ቤቶች ትልቁ ፈተና የሆነው የትምህርት ቀናትን የማሰለስ ችግር ለመቅረፍም ብዙ መስራትን የሚጠይቅ ነው።
መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ የምትሰለፍ አገር ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ክልሉ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ለማድረግ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ ገና ብዙ ጥረት ማድረግ የሚጠይቅ መሆኑንም ተናግረዋል።
በልዩ ፍላጎትና የጎልማሶች ትምህርት ዙሪያ የሚታዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመቅረፍ ክልሉ ብዙ የቤት ሥራ እንዳለበት የጠቀሱት አቶ ብናልፍ፤ ትምህርትን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለዜጎች እንዲዳረስ ለማድረግ በተሰራው ሥራ በመጀመሪያ ደረጃ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ህፃናት ወይም ዕድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱ ህፃናት መካከል 93 በመቶ ያህሉ በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን አስታውሰዋል። የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋንም የታሰበውን ያክል ባይሆንም 40 በመቶ መድረሱን ገልፀዋል።
ከፍተኛ ትምህርትን ለማስፋፋት በተሰራው መጠነ ሰፊ ሥራ በግንባታ ላይ ያሉትን ሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ጨምሮ 10 ዩኒቨርሲቲዎች፣10 የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች፣89 የቴክኒክና ሙያትምህርት ስልጠና ኮሌጆች እና ሌሎች የጤናና የግብርና ኮሌጆች ማስፋፋት መቻሉን አስታውቀዋል።
የሚቀመጡ የመንግሥት አቅጣጫዎችንና የሌሎችን ተሞክሮዎችን እንደ ግብዓት በመውሰድም በክልሉ የሚካሄደውን የትምህርት ሥራ ንቅናቄ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር ትኩረት ሰጥቶ ርብርብ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

አልማዝ አያሌው

Published in የሀገር ውስጥ

ኮሎኔል ሃጎስ ብርሃነ፤

በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ስር የሚወጡ የፈጠራ ውጤቶችንና ሃሳቦችን ወደ ዘላቂ ምርትነት የሚቀይሩ ባለሀብቶች እንደሚያስፈልጉ ተገለጸ።

በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ የደብረዘይት ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ አዛዥ ኮሎኔል ሃጎስ ብርሃነ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ  እንደገለጹት፤በአሁኑ ወቅት በኮሌጁ ተማሪዎች እና መምህራን የሚሰሩ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ወደ ምርት እየገቡ አይደለም።በተጨማሪም ለአገር እና ለግል ጥቅም የሚሰጡ በርካታ የሳይንስ ፈጠራ ሃሳቦችን ወደ ተግባራዊ ስራ ማዋል አልተቻለም።በመሆኑም አትራፊነታቸው እና የሚሰጡት ጥቅም በሳይንስ የተረጋገጡ የምርምር ውጤቶችን በስፋት ለማምረት  በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ያስፈልጋሉ።

እንደ ኮሌጁ አዛዥ ገለጻ፤ የአገሪቷ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ግዢ ላይ ያተኮረ ነው።በመሆኑም አብዛኛው ተቋማት በአገር ውስጥ መዘጋጀት የሚችሉ ምርቶችን  ወደጎን ትተዋቸዋል። ይሁንና ኮሌጁ ይህን አሰራር ለማስቀረት ቴክኖሎጂውን ማሻሻልና ማምረት ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቀይቷል።  በተለይም በዓመታዊ የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን በማዘጋጀት በርካታ የምርምር ውጤቶች እንዲፈልቁ በር ከፍቷል።

በዚህ ረገድ «ባምፐር» የተሰኘ የመኪና ዕቃ «አምፖዛይት» ከተባለ በአገር ውስጥ ከሚገኝ ግብዓት በቀላሉ ማዘጋጀት ተችሏል።በሌላ በኩል የመኪና አደጋ እንዳይደርስ የሚከላከልና ሹፌሮች በሚያሽከረክሩበት ወቅት እንቅልፍ ሲይዛቸው የሚያነቃ መሳሪያ ተሰርቷል።ሌሎችም የፈጠራ ውጤቶች በተለያዩ ጊዜያት በኮሌጁ ለእይታ ቀርበዋል። ይሁንና በተማሪዎች እና መምህራን የሚሰሩ የፈጠራ ውጤቶችን ወደ ምርትነት መቀየር አለመቻሉን ነው የጠቆሙት።

«እነዚህ ፈጠራዎች በተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎች የተመሰከረላቸውና ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች አሻሽለው የተሰሩ ናቸው።በዋጋም ሆነ በጥራት ተመራጭነታቸው ከፍ ያለ ነው» ያሉት ኮሎኔል ሃጎስ፤ይህንንም እድል በመጠቀም የተለያዩ አይነት ፈጠራዎችን ወደምርትነት ለመቀየር የሚፈልጉ አካላት ከተቋሙ ጋር መነጋገር እንደሚችሉ አስታውሰዋል። በዚህም ለአገር እና ለወገን ጠቃሚ ምርቶችን በብቃት ማምረት የሚቻል ሲሆን፤ ከምርቶቹ ከሚገኘው ትርፍ በተጨማሪ አገሪቷ ምርቶቹን ለማስባት የምታወጣውን የውጪ ምንዛሬ በማስቀረት ረገድ ጉልህ ሚና የሚጫወቱ ባለሀብቶችን ማፍራት ይቻላል።በመሆኑም ከመንግስት በተጨማሪ የግል ባለሃብቶች በዘርፉ ቢሰማሩ ትርፋማ እንደሚሆኑ ገልፀዋል።

ኮሌጁ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በሰባት ዙር ባካሄደው የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራና የምርምር ውጤቶች ውድድር በድምሩ 1 ሺ 518 ኢትዮጵያውያን ተሸልመዋል። ይሁንና አብዛኞቹን ፈጠራዎች ወደ ምርት ለማስገባት በተደረገው ጥረት የባለሀብቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ  መሆኑን ነው ያረጋገጡት።

 

ጌትነት ተስፋማርያም

Published in የሀገር ውስጥ

ወይዘሮ ሀረገወይን አፈወርቅ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ በልዩ ስሙ ሽሮ ሜዳ ስላሴ አካባቢ ነዋሪ ናቸው። በወረዳቸው ያለው የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር በጣም ችግር ያለበት መሆኑን ይናገራሉ። አገልግሎት መስጠት እየቻሉም ሰዓት ሳይደርስ ይዘጋሉ። ስኳር ፣ ዘይት የመሳሰሉ ፍጆታዎች እያሉም «የለም  ከግለሰብ ሱቅ ሄዳችሁ ግዙ» እንደሚባሉ ይናገራሉ። በመሆኑም ከሚኖሩበት አካባቢ ርቀው ሄደው ለመግዛት መገዳደቸውን በምሬት ይገልፃሉ። ክትትልና ቁጥጥሩ የተስካከለ አለመሆን፣ የመልካም አስተዳደር  አለመኖር ሌሎች ችግርም ተዳምሮ «ለእንግልት ዳርጎኛል» በማለት ይጠቁማሉ። «የሸማቾች  ህብረት ስራ ማህበራት የተመሰረተው በራሳችን ገንዘብ ቢሆንም ሰራተኞቹ  የግል ተቋማቸው አድርገውታል» እስከማለት የሚያደርስ ምሬታቸውን ይናገራሉ። 

ወይዘሪት ሜሮን ግርማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጀሞ ሶስት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ነዋሪ ናት። የኩፖን አሰራር ከተጀመረ በኋላ ቀድሞ የነበረው ሰልፍ ቢቀንስም የአቅርቦት እጥረት ግን እንዳለባቸው ገልፃለች። የምንፈልገው ሸቀጥ እያለም «የለም» እንደሚባሉ ነው የምትናገረው። «መንግስትም ችግሩን አይቶ መፍትሄ ቢያበጅልን?» ስትል ትጠይቃለች።

 በዘርፉ ሲስተዋል የነበረውን ተግዳሮት ለመፍታት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የማህበራት ዘርፍ የዳሰሳ ጥናት አጥንቷል። በጥናቱ መሰረትም መንግስት ድጎማ በሚያደርግባቸው ምርቶች (ዘይትና ስኳር) ፍጆታው እያለ የለም  የሚባልበት፣ ለህዝብ የመጣውን አቅርቦት በህገ-ወጥ መንገድ ለነጋዴ የሚተላለፍበት፣ ከህብረት ስራ ማህበራት ቸርቻሪ ነጋዴዎች ተረክበው አየር በአየር የሚሸጡበት፣ የህብረት ስራ ማህበራቱም አላግባብ ለሶስተኛ ወገን የሚያስተላልፉበት ሁኔታና መሰል ችግሮች  ተለይተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገብረኪዳን ገብሩ እንደሚገልፁት ሸማቹን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተዘረጋው የክትትል ስርዓት ክፍተት አለበት። በመሆኑም ህብረተሰቡ የድጎማ ምርቶቹ በተገቢው መንገድ ስለማይደርሰው  አገልግሎት አሰጣጡን ያማርራል።

የህብረት ስራ ማህበራቱ ከስኳር ኮርፖሬሽን ከሚያገኙት ስኳር 80 በመቶ የሚሆነውን የሚሰጡት ለቸርቻሪ ነጋዴዎች ሲሆን ለተጠቃሚው  የሚያሰራጩት ደግሞ  20 በመቶ ነው። ሆኖም ቸርቻሪ ነጋዴዎቹ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ካልወሰዱ ለህብረተሰቡ የሚሸጥ ይሆናል። ነገር ግን ነጋዴዎቹ ኮታቸውን ወስደውም ከህብረተሰቡ ጋር በመሰለፍ  ለመቀራመት የሚመጡ ብዙ  መሆናቸውን ይናገራሉ። በመሆኑም በህገወጥ ስራ በተሰማሩት  ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ያስታውሳሉ። ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮችን ለማቃለልም የተሻለ አማራጭ ብሎ ያሰበውን አዲስ አሰራር ወደ ተግባር ለማስገባት ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ  ነው የተናገሩት።

አንዳንድ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት እየሰሩ ያሉት ከተቋቋሙበት ዓላማና ተልዕኮ ውጪ ነው። በዚህ እኩይ ተግባር አንዳንድ ሃላፊነት የማይሰማቸው አመራሮችና  ፈፃሚዎች ተሳታፊ  እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ሆኖም ተጠያቂ የማድረግ ሂደቱ ጫፍ የደረሰ እንዳልነበረ ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ግን ገንዘቡ ኦዲት እንዲደረግ፤ አመራሮቹም በህዝቡ ተጠያቂ እንዲሆኑ፤ ጥፋት የተገኘባቸውም የህግ እንዲሁም የዲስፕሊን እርምት እርምጃ እንዲወሰድባቸው እየተደረገ መሆኑን ያስረዳሉ።

ለአብነት ያነሱትም  በአቃቂ ቃሊቲ  ክፍለ ከተማ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በመኪና ግዢ ስም አላግባብ ወጪ ማድረግና የህዝብ ሀብት ማባከን፤  ነጋዴው በተወሰነለት ቀነ ገደብ ኮታውን ካልወሰደ  መመሪያው በሚያስቀምጠው አሰራር  መሰረት ተግባራዊ ከማድረግ ውጪ ከነጋዴ ጋር በመደራደር አየር በአየር የመሸጥ ሂደቶችም ተስተውለዋል። በተመሳሳይ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ  መርካቶ ሶስት ኩንታል ስኳር አለአግባብ ሲሸጥ ተይዟል። 18 ብር መሸጥ የነበረበት ስኳር ከ25 እስከ 30 ብር የመሸጥ ሁኔታዎች ተስተውለዋል። በመሆኑም  ችግሮችን በፍጥነት ለመፍታት ከየካቲት  ወር አጋማሽ ጀምሮ አዲስ አሰራር እንደሚጀመር ነው የጠቆሙት።

ምክትል ኃላፊው እንደሚሉት ችግሮች የተፈጠሩት ነጋዴውና ነዋሪውን ስላልተሳሰሩ ነው። በመሆኑም በአዲሱ አሰራር ቸርቻሪ ነጋዴውንና ነዋሪውን ከሸማች ህብረት ስራ ማህበራቱ ፣ እንዲሁም ነዋሪውን ከቸርቻሪ ነጋዴው ጋር እንዲተሳሰሩ ይደረጋል። በከተማ ደረጃ ወጥ የሆነ ኩፖን በማዘጋጀት ነዋሪውን ከአንዱ  ቸርቻሪ ነጋዴ ጋር ብቻ በማስተሳሰር ችግሩ እንዲቀረፍ ይደረጋል። ለቸርቻሪ ነጋዴውም የአካባቢው ነዋሪ ተቆጥሮ ይሰጡታል። አንድ ቤተሰብም በወር እስከ 10 ኪሎ ተኩል ስኳር እንዲያገኝ መንግስት ድጎማ አድርጓል። በመሆኑም ቀደም ሲል በከተማዋ ሲከፋፈል የነበረው 112 ሺ ኩንታል ወደ 120 ሺ ኩንታል ከፍ እንዲል ተደርጓል።

የምናስተሳስራቸው ነጋዴዎች «በጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር የምንመራ  ከሆነ አናሰራጭም» የሚሉ አስተሳሰቦች  እንዳላቸው እየታየ ነው። ነገር ግን ይህን ለማለት የንግድ ህጉ አይፈቅድላቸውም። አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋሙ በመሆኑ ህጋዊ በሆነ መንገድ ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው። ይህ ካልሆነ ግን  በህጉ  መሰረት ተጠያቂ እንደሚደረጉ ነው  አቶ ገብረኪዳን የገለፁት ።  

 

ዜና ሀተታ

ፍዮሪ ተወልደ

Published in የሀገር ውስጥ
Monday, 13 February 2017 18:34

የሴቷ ፈተና

ባሳለፍነው ጥር ወር፣እናትነትን ከፍ ከፍ ያደረጉ ንግግሮች በስፋት ተደምጠዋል፡፡ የጥር የጤናማ እናትነት ወር «ርህራሄና አክብሮት ለእናቶች» በሚል መሪ ቃል የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እናትነትን የሚመለከቱ መግለጫዎች ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን ማርች 8 የሚከበረውም በያዝነው የካቲት ወር ነው፡፡ የተለያዩ ዝግጅቶች ተደርገዋል፡፡ በሴቶች ላይ ስለሚደርስ ፈተና ለማውራት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው። የሴቶች ጉዳይ  ትልቅ አጀንዳ ነው፡፡ ለእናትነትና ለአጠቃላይ ሴትነት  ክብር መስጠት አለብን፡፡ የእናቶችን ጤና ከእርግዝና እስከ ወሊድ ያለውን ጊዜና ከወሊድ በኋላ ልጅ በማሳደጉ ረገድ ላለባቸው በርካታ ፈተናዎች ዕውቅና መስጠት አለብን፡፡ ይህን ሁሉ መከራ አይታ ወልዳ አሳድጋ ለቁም ነገር ላበቃች እናት የሚገባት ክብር እጅግ የላቀ መሆኑን አምነን መቀበልና በተግባርም ማሳየት አለብን፡፡

 በህብረተሰባችን በተለይም በወጣቶቻችን ዘንድ ይህ የእናቶች ክብር ጉዳይ ትኩረት አላገኘም፡፡ የሁሉም ሰው አፍ መፍቻ እስኪመስል ድረስ ንግግራችን ሁሉ እናቶችን በመሳደብና በማዋረድ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ከገጠር ለመጡ ወጣቶችማ የአራዳነት ማሳያ እየመሰላቸው የእናትን ክብር የሚያጎድፍ፣ ለጆሮ የሚሰቀጥጥና ለፅሁፍም የማይመች ስድብ አፋቸው ላይ የተጣበቀ ይመሰላል፡፡ ቃሉ ራሱ ለአገራችን ባዕድ ነው፡፡ ፍፁም ብልግና ነው፡፡ የእናቶችን ክብር  የሚፃረር አሳፋሪና አዋራጅ ንግግር ነው፡፡ ለእናትነት የሚከፈለው ውለታ ይህ አይደለም፡፡ ጥፋቱ ተሳዳቢዎቹ ላይ ብቻ ሳይሆን እንዲህ አይነቱን ስድብ እየሰማ ዝም ብሎ የሚያልፈውም ህብረተሰብ ጭምር  ነው፡፡

የበፊቱ ትውልድ  ፀያፉን ስድብ ቢሰድቡት «እንዴት አንተ እምዬን» ብሎ መውዜሩን ይዞ ካልገደልኩ ይል ነበር፡፡ ስንት ሽማግሌ ተጠርቶ፤ ስንት ቄስ መጥቶ እግር ተስሞ ነበር ይቅርታ ተጠይቆ እርቅ የሚወርደው። እናትን መስደብ ፀያፍ ነው፡፡ አሁን ግን ከተማው ሁሉ በፀያፉ ስድብ ተሞልቷል፡፡ ፖሊሶችና ደንብ አስከባሪዎችም እየሰሙ «እንዳልሰሙ» ሆነው ያልፉታል፡፡ ይህን አይነቱን ፀረ-እናትነት የብልግና ስድብ የሚያስቆምልን ማን ነው? አደብ የሚያስዝልን የትኛው ህግ ... የትኛው አካል /ተቋም ነው፡፡ ማህበራዊ ተቋማት ለምሳሌ እድሮች እንዲህ አይነቱን ስድ-አደግነት ለመግታት ከቤት ጀምሮ እስከ አደባባይ ያሉ ልጆቻቸውን ስርዓት ለማስያዝ አቅም ያንሳቸው ይሆን? ለመሆኑ በየስብሰባዎ ቻቸው ላይ ይህን የእናትነትን ክብር የሚነካ ጉዳይ አንስተው ተነጋግረውበት ያውቃሉ? ወይስ ይህንንም ችግር መንግስት እንዲፈታልን እንፈልግ ይሆን? የገዛ ልጆቻችንን ለመግራትና ትክክለኛውን ባህላዊ ዕሴት ለማስጨበጥ እራሳችን /ወላጆች መትጋት አለብን፡፡ ርህራሄና አክበሮት ለሴቶች ይሁን!

በአጠቃላይ በሴቶች ላይ በተለይም በእናቶች ላይ የሚሰነዘረውን ፀያፍና አዋራጅ ንግግር ማስቆም ካልተቻለ ትምህርት ቤቶች የእምነት ተቋማት፣ማህበራዊ ቡድኖችና  ሲቪክ ማህበራት እዚህ ላይ መስራት ካልቻሉ በሴቶች ላይ የሚደርስ የአደባባይና የቤት ውስጥ ጥቃቶች በዓይነትና በመጠን እየሰፉ ይመጣሉ፡፡

በዓለማችን ውስጥ በሴቶች ላይ የሚደርሱ በርካታ የፈተና ዓይነቶች አሉ፡፡ የአንዳንዱ ፈተና መንስኤ ኋላቀርነት ነው፡፡ ሌላው አጉል ባህል ልማድና ወግ ነው፡፡ ለምሳሌ ጥንታዊ የህንድ ባህል አለ፡፡ የወር አበባ /ቹዋፓዲ- chhuapadi ላይ ያለችን ሴት የማግለልና ከዋናው ቤት ወጥታ በጭቃ ቤት ውስጥ እንድትከርም የሚደረግበት ባህል አለ፡፡ እንደ ርኩስ ይቆጥሯታል፡፡ ምንም ነገር መንካት አትችልም፡፡ ደብተርና መጽሃፍ መንካት ሀጢአት ነው ስለሚባል አታነብም ትምህርት ቤት አትሄድም፤ በተባይ የተሞላና የተሳቢ አውሬዎች ስጋት ባለበት ጭቃ ቤት ውስጥ ለሳምንት ያህል ትቆያለች፡፡

የወር አበባ በ12 ዓመቷ ካየች ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በየወሩ በዚህ አይነት እየተሰቃየች ትኖራለች ማለት ነው፡፡ የህንድ መንግስት ይህ አጉል ባህል እንዲቀር በ2005 አዋጅ አውጥቷል። ነገር ግን በብዙ ግዛቶች መሬት ወርዶ ተግባራዊ አልሆነም፡፡ በርካታ ሴቶች በቤተሰባቸው አመለካከት ተስፋ ቆርጠው ቤት ለመከራየት ይሞክራሉ፡፡ ቤት አከራዮች ደግሞ አያከራዩዋቸውም ከተከራዩም  ምድር ቤት ነው የሚያከራዩዋቸው፤ ይህም ሆኖ የውኃ ቧንቧ መንካት አትችልም፡፡ ታረክሰዋለች ስለሚባል በዚህ ሁኔታ ራሳቸውን ያጠፉ  ሴቶች ቁጥር ብዙ ነው ፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ነገሩ በእኛም አገር ነበር አልፎ አልፎም አለ። በተለይ የኦሪት እምነት ተከታይ ፈላሾች ዘንድ በስፋት ነበረ፡፡ «አሊያህ ቤት» በተባለው የደራሲ መስፍን አሰፋ መጽሐፍ ከገጽ 140-142 የተጻፈው ይህን የሚያረጋግጥልን ነው ፡፡ በወር አበባቸው ጊዜ ሴቶችን እስከ 7 ቀን ድረስ አግልሎ በጭቃ ቤት ውስጥ የማቆየት አሰራር  የትኩቶ/ኒዳ ሥርዓት ይባላል፡፡ ሴቷ የምትከርምበት ቤትም  «የመንፃት ቤት» ይባላል፡፡ የሰሜን ሸዋ ቤተ እሥራኤላውያን ዘንድ በጥብቅ ይከበር ነበር፡፡ ትዕዛዙ አምላክ ለሙሴ በሰጠው ህግ ላይ የሰፈረ ነው፡፡ (ዘሌዋውያን 15፡19-33 ) የሆኖ ሆኖ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ኃይማኖታዊ ምክንያቶች የተነሳ ሥርዓቱ እየቀረ ነው፡፡ አሁን እኛ አገር ያሉ ዋና ዋና የአጉል ባህል መገለጫዎች የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ ዕድሜ ጋብቻ   ናቸው ፡፡

ወደ አፍጋኒስታን ብትሄዱ አይታችሁ ሰምታችሁ የማታውቁት አይነት ፈተና በሴቷ ላይ ሲደርስ ያጋጥማችኋል፡፡ ዛሪና ትባላለች፣ የ23 ዓመት ወጣት ናት በ13 ዓመቷ ባል አገባች ባሏ እጅግ በጣም ቀናተኛ ነው፡፡ ቤተሰቧን ሄዳ ለመጠየቅ አይፈቀድላትም በሆነው ባልሆነው ይጠረጥራታል፡፡ በመጨረሻም ሌሊት ከመኝታዋ  ቀስቅሶ እጇን ከጀርባዋ ጠፍንጎ አስሮ በኩሽና ቢላዋ ሁለት ጆሮዋን ሙልጭ አርጎ ቆርጦ ጣለባት፡፡ የቆየ ወሬ አይደለም ፡፡ አሁን ፌብሯሪ 2017 የተፈፀመ ነው፡፡ ባልየው ለጊዜው አልተያዘም፡፡

እዛ አካባቢ በተራ የቤተሰብ ጠብና ጥርጣሬ የተነሳ የሴቷን አፍንጫና ጆሮ ቆርጦ መጣል ያለማቋረጥ የሚታይ ክስተት ነው፡፡ ልክ የዛሬ ዓመት ( Jan. 2016 ) ራዛ ጉህል የተባለች ሴት ባሏ አፍንጫዋን በቢላዋ ቆርጦ ጥሏል፡፡ ከዚህ ጥቂት ወራት በኋላ ደግሞ አንዲት ሴት ባሏ ደብድቦ ገድሏታል፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ( Nov. 2015 ) አመንዝራ ተብላ በሀሰተኛ የዝሙት ወንጀል የተከሰሰች ሴት በድንጋይ ተወግራ ሞታለች፡፡ በዚያው ዓመት አንዲት የካቡል ሴት ቅዱሱን መጽሀፍ አቃጥላለች ተብላ በሀሰተኛ ክስ በድንጋይ ተወግራና በእሳት ተቃጥላ ተገድላለች፡፡ ይህም ከባል በኩል በሚመጣ /በሚደረግ ጥቆማ የተፈፀመ ነው፡፡

የሴቷን ፈተና የእሷን ችግር፣ የእሷን ቃል የሚሰማ የለም፡፡ ከባህሉና ከልማዱ የተነሳ ሁሉም የሚፈርደው በሴቷ ላይ ነው፡፡ እናትነቷ፣ እህትነቷ፣ ሚስትነቷ ፣ ልጅነቷ አይታይላትም፡፡ ብዙ አገሮች ሴቶችንና ህፃናትን ከጥቃት የሚከላከል የቤተሰብ  ህግ የላቸውም፡፡ያላቸውም ቢሆኑ በጥልቀት አይሄዱበትም፡፡ ሰለጠኑ የሚባሉት አገሮች ሩሲያን ጨምሮ የቤተሰብ ህግ አስፈላጊነት አይታያቸውም፡፡ እንዲያውም በቤተሰብ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ እንደመግባት ይቆጥሩታል፡፡

የሩሲያው የተለየ ነው፡፡ በቅርብ የወጣን የአንዲት  ሴት ታሪክ መሰረት አድርጎ ቢቢሲ ያቀረበው ዘገባ ጉድ አሰኝቷል፡፡ ሲትየዋ እንደተናገረችው ባሏ በየቀኑ ሲወጣም ሲገባም ይደበድባታል፡፡ ከሁለተኛ ፎቅ ላይ ገፍትሮ ጥሏት የወገብ አጥንቶቿ ረግፈዋል፡፡ በዊልቼር ጋሪ እየሄደች እያለች እንኳ ድብደባው አልተቋረጠም፡፡ የሁለት እግሮቿ አጥንቶችና ሁለት እጆቿ ተሰባብረው ከጥቅም ውጭ ሆነዋል፡፡ ለፖሊስ ሄዳ አመልክታለች፡፡ «እኛ በቤተሰብ ጉዳይ ጣልቃ አንገባም» ብለዋታል፡፡ ባልየውን ጠርቶ የጠየቀው ፖሊስ የለም።  በዚህ ዓይነት በዚያች አገር በየወሩ የ600 ሴቶች ህይወት ይጠፋል፡፡ ይባስ ብሎ የሩስያ የታችኛው ምክር ቤት (Duma) የቤተሰብን ጉዳይ ከወንጀል ህጉ ጋር የሚያያይዙ አንቀፆችን አውጥቶ ጥሏል፡፡

በቤተሰብ አካላት መካከል የሚነሳ ጠብና በዚህም ምክንያት ሊደርስ የሚችል ጉዳት በወንጀል አያስጠይቅም፡፡ ከሞት በመለስ ያለው ጉዳት ሁሉ የቤተሰብ ጉዳይ ነው ተብሎ ይታለፋል፡፡ ይህች ሴት ከጎኗ የሚቆምላት ሰው የላትም፤ የቤተሰብ ጉዳይ ነው እየተባለ ጣልቃ የሚገባ የለም፡፡ ህጉም ለእርሷ የሚያደርገው እገዛ የለም፡፡ የመጨረሻ ዕድሏ በድብደባ በረሃብና በችግር ተቆራምዳ ከሰውነት ውጭ ስትሆን ፈረንጆች የለመዱት ማስወገጃ አለ፡፡ ይህም ጨለማን ተገን አድርገው የቆሻሻ ገንዳ መጣያ አጠገብ ወይም በአንዱ የእምነት ተቋም አጥር ስር ወስደው መጣል ነው፡፡ ሌላ ቃል የለውም፡፡

በዚህ ረገድ በቅርብ ያለኝ መረጃ አንድ ወንድምና እህት በሽተኛ አባታቸውን ለመንከባከብና የመድኃኒት ወጪውን መሸፈን ስላልፈለጉ አባታቸውን ለማስወገድ ወሰኑ የሚያስወግዱት በመግደል አይደለም፡፡ ራቅ ወዳለ ቦታ ወስዶ በመጣል (dumping) እንጂ፡፡ አባትየው በሽተኛ ነው፡፡ መናገር አይችልም ፡፡ ልጆቹ አባታቸውን ከሎስ አንጀለስ ይዘው እንግሊዝ አገር ወስደው አንድ ጨለማ የምድር ውስጥ ጉሮኖ ውስጥ  ወትፈውት ሄዱ፡፡ ሶስት ሆነው ሄደው ሁለት ሁነው ተመለሱ ከብዙ ቀናት በኋላ የእንግሊዝ ፖሊስ ወሬው ደረሰው፡፡ ማንነቱ የማይታወቅ፣ መታወቂያም ሆነ ፓስፖርት የሌለው ፣መናገር  የማይችል ሰው መኖሩን አወቀ። በስንት መከራ በፖሊስ ምርመራ ሰውየው ስሙን ብቻ መናገር ቻለ፡፡ ድምፀቱ አሜሪካዊ መሆኑን ጠቆመበት ምርመራው ቀጥሎ የአየር መንገዱ የተሳፋሪዎች ዝርዝር ሲታይ ሰውየው ከሁለት ልጆቹ ጋር ወደ ለንደን የመጣ ነው፤ ልጆቹ ብዙም ሳይቆዩ ወደ አሜሪካ ተመልሰዋል፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ብቻ በመጨረሻ ልጆቹ አባታቸውን መጣላቸው ተረጋገጠ፡፡

ይህ አሁን ባሳለፍነው ጥር ወር 2009ዓ.ም የመጨረሻ ሣምንት የተከሰተ ድርጊት ነው፡፡ የሴቶቹም ሁኔታ የባሰ ነው፡፡ በየአገሩ ብዙ ነገር አለ፡፡ የእኛ አገር በስንት ጣዕሙ! ዛሬ ላይ ሆነን አሁን መስራት ያለብንን ስራ ተዘናግተን ወይም በቸልተኛነት ብናልፍ ነገ በሴቶቻችን ላይ የሚደርሰውን ፈተና ለመቋቋም ችሎታ አይኖረንም፡፡ ማጠፊያው ያጥረናል፡፡ አሳታፊነት … ተጠቃሚነት… አካታችነት ስለሚባለው ነገር ሳይሆን በቀጥታ መሬት ወርዶ ከቅጠል ተሸካሚዋ ሴት… ከጉልት ቸርቻሪዋ ቤት በየጎዳናው  በየታክሲ ማዞሪያው ወይም ሰው በተሰበሰበበት ማንኛውም ቦታ ቡና፣ ሻይና ፓስቲ እያዞረች በመሸጥ ስለምትተዳደረው ያቺ ምስኪን ሴት የወደፊት ሳይሆን የአሁን ዕጣ ፈንታ መነጋገር አለብን፡፡

እነዚህ የደላቸው አይደሉም ስንል ግን በየመስሪያ ቤቱ ተቀጥረው የሚሰሩት  «ተመችቷቸዋል» ማለታችን አይደለም።  ስለእነርሱም ቢሆን ያለን መረጃ በቂ ነው፡፡ ለምሳሌ የመንግስት አጠቃላይ የመቅጠር አቅም ከአንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ  አይበልጥም፡፡ ከዚሁ ቁጥር ውስጥ ሴቶች 500ሺህ ቢሆኑ ነው ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 400ሺህ የሚሆኑት ሴቶች  በዝቅተኛ የሥራ መደብ ላይ የተሰማሩና ዝቅተኛ ተከፋይ ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ የመድልኦና የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባዎች ናቸው ፡፡

በተለያዩ አገር አቀፍና ዓለምአቀፍ ሰነዶችና ጉባኤዎች ላይ አድሏዊ አሠራሮችን የሚከለክል ፖሊሲ ቢኖርም መሬት ሲወርድ ግን ብዙ መሻሻል የሚታይበት አይደለም፡፡ ሴቶች በሥራቸውና በህይወታቸው ውስጥ የበታችነት እንዳይሰማቸው፣ በራስ መተማመን እንዲኖራቸው ከባህልና ከልማድ ጠፋሪ ማነቆዎች ውጭ ሴቶችን ከግባቸው እንዳይደርሱ የሚያግዳቸው የማይፈታ ተግዳሮት የሌለ መሆኑን እንዲያምኑ ማስቻልና ማብቃት ያስፈልጋል፡፡ የቤተሰብ ጠብንና በስሜታዊም ሆነ ቁሳዊ ሰበቦች በሚነሱ ግጭቶች በሴቶችና በህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቀረት በቤተሰብ ህጉ ዙሪያ ከፍተኛ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መስራት ይገባል፡፡

የቤተሰብ ጉዳይ ሆነም አልሆነ በሴቶች ላይ አንዳችም አካላዊና ስነ ልቡናዊ ጉዳት መድረስ የለበትም፡፡ በቤተሰብ ጉዳይ ጣልቃ አንገባም በሚል እጃችንን አጣጥፈን የምንመለከተው ጉዳይ አይኖርም። የሴቶችና የህፃናት ጉዳዮች በሙሉ የእኛ የመላው ህዝብ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ከሌሎች አገሮች /ሰልጥነዋል ከሚባሉት/ አገሮችም አንፃር ሲታይ የእኛ አገር  የቤተሰብ አስተዳደር ልማድና ባህል የተሻለ ነው በጋራ እየተጋፈጥን ካለው የጋራ ጠላታችን ከሆነው ድህነት በስተቀር የሴቶችና የህፃናት አያያዛችን በፖሊሲ ደረጃ ብዙም የሚነቀፍ አይደለም፡፡ ችግር የለም ማለት አይደለም፡፡ አብዛኛው ግን በንቃተ ህሊና በግንዛቤ ዕድገት የሚፈታ ነው፡፡ ሴቷ ጤናማ እናት የምትሆነው የልማት አጋር የምትሆነው አካላዊና ስነ-ልቡናዊ ጤንነቷ ሲረጋገጥ ነው፡፡

ግርማ ለማ

Published in አጀንዳ

 

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከሕንፃ ግንባታ ጥራት ጋር በተያያዘ  ባጋጠመው የሕንፃ መሰነጣጠቅ  350 ተማሪዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን አስታወቀ። ትምህርት ሚኒስቴር ችግሩን አምኖ ለመፍትሔው ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑን ገልጿል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር  ሀብታሙ ተካ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንዳስታወቁት በግንባታ ጥራት ላይ ከፍተኛ  ችግር በመኖሩ ምክንያት የ350 ተማሪዎች መኖሪያ  የነበረው ሕንፃ  ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆን ተደርጓል።

የዩኒቨርሲቲው ግንባታ ከዲዛይን ጀምሮ ችግር ያለበት በመሆኑ አምስት ዓመት እንኳን ሳያገለግል ከፍተኛ የመሰነጣጠቅ አደጋ እንዳጋጠመው ጠቅሰው፤ ሕንፃው በማንኛውም ወቅት ሊፈርስ ስለሚችል በተማሪዎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በሚል   ተማሪዎች እንዳይጠቀሙበት መደረጉን ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፤ ይሄ የሚያሳየው በጥራት ላይ ከፍተኛ ችግር መኖሩን ነው። የውሃ ፍሳሹም በአግባቡ የማይወርድና ከሁለተኛ ፎቅ በላይም አይወጣም። ትልቁ ችግር  በዲዛይን ላይ በአግባቡና ጥንቃቄ  ባለው መልኩ ባለመሠራቱ  ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን  ነው የጠቆሙት።

አቅም የሌላቸው ተቋራጮች  እየገቡ ከፍተኛ የጥራት ችግርና የግንባታ መጓተት እያጋጠመ  መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፤ በዚህም ወደ መካሰስ የሚገባበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል። በተመሳሳይ ችግር ሦስት ጊዜ ፕሮጀክቶች ውድቅ ሆነው እንደገና ወደ ሌላ የተገባበት ሁኔታ እንደነበር ተናግረዋል።

የፕሮጀክቶች መዘግየት በተማሪዎች ቅበላ ወቅት አሉታዊ ተፅዕኖ እያስከተለ ነው። ይሄ  እንደ አገርም የሀብት ብክነት የሚያስከተል መሆኑን አመልክተዋል። በሕንፃው ላይ ያጋጠመው የመሰነጣጠቅ ችግር የሥራ ተቋራጩ፣ አማካሪውም ሆነ ዲዛይነሩ ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ ባለመሠራቱ የሚያጋጥም  መሆኑንም ገልጸዋል።

ለዩኒቨርሲቲው የግንባታ ጥራት  መጓደል መነሻ ምክንያቱ ቶሎ ወደሥራ ለማስገባት ሲባል የጥድፊያ ሥራ መሠራቱ  አሁን ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን  ጠቅሰዋል። ቀደም ሲል በጥራት ላይ የነበረው ችግር አሁንም በአዳዲሶቹ ፕሮጀክቶች ላይም አልተቀረፈም። በመሆኑም ለቀሪ ሥራዎች ዩኒቨርሲቲው፣ተቋራጩና  አማካሪው በጋራ ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሁለተኛው ትውልድ  ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ የተሠራው  በትምህርት ሚኒስቴር ባለቤትነት፣ በጂአይዜድ ገንቢነትና  ኤም ኤች በተባለው ድርጅት  አማካሪነት መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፤  በወቅቱ የነበሩት ግንባታዎች  ከፍተኛ  የጥራት ችግር እንደነበረባቸው በተደጋጋሚ ማሳወቃቸውን ጠቁመዋል። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ከሕንፃው ውጪ የውሃ ማጠራቀሚያ በመገንባት ለተማሪዎች አገልግሎት እንዲሰጥ መገደዱን ገልጸዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር የኮሙንኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ ጣፋ  እንደገለጹት የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ  የተማሪዎች መኖሪያ ሕንፃ የተሰነጣጠቀው በተወሰነ ደረጃ ከግንባታ ጥራት  ጋር ተያይዞ ቢሆንም  ዋናው ችግር ግን  የመሬቱ መንሸራተት  መሆኑን ጠቁመዋል።

የሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግንባታ ሲካሄድ አፈሩ ተመርምሮ  መሆኑን አስታውሰው  የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲም የአፈሩ ሁኔታ ተረጋaግጦ ግንባታው መካሄዱን ተናግረዋል። ሆኖም ግን አፈሩ የሚሸሽ በመሆኑ  ችግሩ መፈጠሩን  አመልክተዋል። ችግሩን ቀድሞ ማወቅና  በተወሰነ ደረጃም  የክትትል ማነስ እንደነበር አምነዋል።

አሁን ተማሪዎች በሕንፃው ውስጥ እንዳይኖሩ መደረጉንና በቀጣይም መፍትሔው ምን መሆን አለበት በሚለው  ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው  ጋር በጋራ በመነጋግር ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛው ትውልድ ከሚባሉት 13ቱ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ነው።  በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ  ዘመን መጨረሻ 17 ሺ ተማሪዎችን የመቀበል  ዕቅድ አለው።

 

አልማዝ አያሌው

    

Published in የሀገር ውስጥ

የሴቶች በፖለቲካ ውሳኔ ሰጭነት የመሳተፍ መብት እ.አ.አ በ1948ቱ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ ዕውቅና አግኝቷል፡፡ የመግለጫው አንቀጽ 2 እና 21 ሴቶች በጾታቸው ምክንያት መድልኦ ሳይደረግባቸው የፖለቲካ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙ ደንግጓል፡፡ እ.አ.አ. በ1966 የወጣው የፖለቲካና የሲቪል መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት በመግለጫው የተጠቀሰውን የሴቶች በመንግሥትና የፖለቲካ ሕይወት ያለምንም መድልኦ የመሳተፍ መብታቸውን አጠናክሮ ደንግጓል፡፡

የተባበሩት መንግስታት 17 ዘላቂ የልማት ግቦች መካከል  በአምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የፆታ እኩልነትን ማስፈን፣ሴቶችና ልጃገረዶችን ማብቃት አንዱ ነው።ድርጅቱ እ.አ.አ. በ2015 በአሜሪካ ኔውዮርክ ከተማ  ያወጣው እቅድ  እ.አ.አ. 2030 ድረስ በዓለም ላይ ሴቶች ከወንዶች እኩል መብት እንዲኖራቸው የጊዜ ገደብ አስቀምጧል። 

በአገራችን ካለው የሕዝብ ብዛት ሴቶች ግማሹን ቁጥር እንደሚይዙ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄድ ህዝብን የሚመለከት ማንኛውም እንቅስቃሴ እነዚህን የህብረተሰብ ግማሽ አካላት ግምት ውስጥ ያስገባ ሊሆን ይገባል፡፡ሴቶችን የማያሳትፍና እኩል ተጠቃሚ የማያደርግ ማናቸውም ዓይነት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ለውጤት እንደማይበቃ ሊታበል የማይችል ሀቅ ነው፡፡

በአገራችን የሴቶች ትግል ትልቁ ድል እንደሆነ በሚታመንበት የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት መሠረታዊ የሆኑት የሴቶች መብቶች መከበራቸው፣ የኢፌዴሪ የሴቶች ፖሊሲ መውጣቱ፣ በፌዴራልና በክልል መንግስታት የሴቶች ጉዳይ አደረጃጀት መፈጠሩ፣የቤተሰብ ህግ መጽደቁ፣ የወንጀለኛ ህግ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ በደሎችን ለመግታት በሚያስችል መልክ መሻሻሉ…ወዘተ የሴቶችን ጥያቄ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖራቸው አይካድም፡፡በሌላም በኩል በትምህርት፣በጤናና በሌሎችም የልማት መስኮች የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ የተከናወኑት ሥራዎችና የተገኙት ውጤቶች አበረታች   ናቸው፡፡

በአገራችን የተደረጉ የፓርላማ ምርጫዎችን ለመቃኘት ብንሞክር በየምርጫ ዘመኑ ከፍተኛ የሚባል መሻሻሎችን እናያለን።ለአብነትም  በመጀመሪያው ምርጫ ከ547 የፓርላማ ወንበር  13 (2ነጥብ7በመቶ)  ከነበረበት እድገት እያሳየ መጥቶ አምስተኛው  ምርጫ ላይ ከ547 መቀመጫዎች ውስጥ 213 ወይም 38ነጥብ9በመቶ  መድረሱ ሴቶች በፖለቲካው መስክ ያላቸው  ተሳታፊነት እየጨመር መምጣቱን ያሳየናል። በዚህ ፍጥነት የሴቶች ተሳትፎ የሚቀጥል ከሆነ  የተባበሩት መንግስታት በ2030 የሴቶችን ከወንዶች እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚ ለማድረግ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት የሚቻልበት እድል ሰፊ ይሆናል።

 የሴቶች ውክልና ከጨመረ የሴቶች ብቃት መጨመሩ አይቀርም፡፡ የሴቶች ብቃት ከጨመረ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው የጾታ መድልኦ አመለካከት በሒደት የሚቀረፍ ይሆናል። አገሪቱ የተነሳችበትን በጾታ መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ  ለማሳካትም ያስችላል፡፡በሁሉም ኅብረተሰብ እንደሚታየው ሴቶች ሕፃናትን የማሳደግና የመንከባከብ ድርሻቸው ሰፊ በመሆኑ የሴቶቹ የውሳኔ ሰጪነት መሳተፍ ሕፃናቱንም መጥቀሙ አይቀርም፡፡የሴት የፖለቲካ ተወካዮች ከሴቶች መብት በተጨማሪ የሕፃናትም መብቶች እንዲከበሩ በተሻለ እንዲሰሩ እድል ይፈጥርላቸዋል፡፡

በፓርላማ ያለው የሴቶች ተሳትፎ እድገት ቢያሳይም በሌሎች ከፍተኛ የፖለቲካ መዋቅሮች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ግን አናሳ ነው። ከተለያዩ ጥናቶች ለመገንዘብ እንደሚቻለው ሴቶች ወደ ፖለቲካ አመራር ሰጪነት እንዳይመጡ የሚያደርጉ ምክንያቶች ብዙ ናቸው፡፡የመጀመሪያው ባህላዊና ኋላቀር አስተሳሰብ ነው፡፡ ሴቶችን ከአደባባይ ሥራ ይልቅ በጓዳ የሚገድብ ባህል ባለበት ሀገር ሴቶች ከልጆች አስተዳደግ ውጭ ያላቸውን ወይም የሚኖራቸውን ሚና የሚቀበል አሠራር መገንባት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ባህል በወንድ የበላይነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ይቅርና እኩልነታቸው የሚገዳደሩ አስተሳሰቦች ይበዙበታል፡፡

ሌላው ሴቶች ወደ አመራርነት እንዳይወጡ ተጽዕኖ ከሚፈጥሩባቸው ችግሮች መካከል ከራሳቸው የሚመነጭ አመለካከት ነው። ካለባቸው ተደራራቢ የቤት ውስጥ የስራ ጫና በመነሳት ኃላፊነትን ለመወጣትና ለመቀበል ድፍረት አለመኖር፣ ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች፣ በትምህርትና ስልጠና አለመብቃት፣ እንዲሁም የውጪው ተጽዕኖዎች ናቸው።  በሴቶች ብቃት አለማመን፣ በኃላፊነት ቦታም  ሲቀመጡ ስህተት መፈለግ በስፋት ስለሚስተዋሉ እነዚህን የተዛነፉ አመለካከቶች ፈጥኖ ማስተካከል ይገባል።

ሴቶችን በውሳኔ ሰጪነት ለማብቃት ሁሉም ተቋማት የተጠናከረ ሥራ ሊሰሩ ይገባል።በየተቋማቱ የተዋቀሩት የሥርዓተ ጾታ ክፍሎች በአፈፃጸም ደረጃ ውስንነት ማስተካከልና የሴቶችን አቅም በማጎልበት ለአመራር ሰጪነት በማብቃት በኩል የሚስተዋልባቸውን ክፍተቶች ከወዲሁ ሊያስተካክሉ ይገባል።

በየደረጃው የሴቶችን ፎረሞች የማቋቋምና የመደገፍ ጅምር ስራዎች የሚያበረታቱ ቢሆኑም የሚፈለገውን ያህል ባለመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል።ሴቶችን ማብቃት አመለካከትን የመስበር ጉዳይ እንጂ የመመሪያ፣ደንብና አዋጅ ጉዳይ አይደለም።የስርዓተ ጾታ የስራ ክፍሎችን ማቋቋም፣አደረጃጀት እና በጀት ላይ የሚነሱ ችግሮችን  መፍታት ከተቻለ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል።

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን፤

ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እያከናወነች ያለውን ስኬታማ ተግባራት የተለያዩ ዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙሃን በድረ ገጾቻቸው ለንባብ አብቅተዋል። ባሳለፍነው ሳምንትም የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ስለኢትዮጵያ ከዘገቡት መካከል የተወሰኑትን  እንዳስሳለን፡፡

 

የተባበሩ መንግስታት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዛፎችን በኢትዮጵያ ሊተክል ነው

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በሚገኙበት ካምፕ አካባቢ የደን መራቆትን ለመከላከል  ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዛፎች ለመትከል ማቀዱን የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት አስታውቋል። ችግኞቹ  በ150 ሄክታር ላይ የሚተከሉ ሲሆን ይህም የሚደረገው  በጋምቤላ ክልል በየጊዜው እየጨመረ ለመጣው የስደተኞች ቁጥር የኃይል ፍላጎትን ለማቅረብ እንዲያስችል በማሰብ  ነው።

በደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ግጭት ከተቀሰቀሰበት እአአ 2013  ጀምሮ በጋምቤላ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ  300 ሺ ለሚሆኑ  ሴቶችና ህጻናት መኖሪያ ተሰጥቶአቸዋል፡፡ስደተኞቹ ምግብ ለማብሰል የሚጠቀሙት  የማገዶ እንጨት በመሆኑና ከብዛታቸው አንጻር በየቀኑ ዛፎቹ እየተመናመኑ ሄደዋል። ይህም የአየር ንብረት መዛባት እንዲመጣ ከማድረጉ በተጨማሪ ሴቶች ለእንጨት ለቀማ በወጡ ቁጥር  ለአስገድዶ መደፈር  እንደሚጋለጡ የድርጅቱ የሃይልና እጽዋት ባለሙያ ይናገራሉ፡፡ ድርጅቱም ይህን ችግር ለመግታት  በአካባቢው ቶሎ የሚደርሱ እንደባህርዛፍ የመሳሰሉ ዛፎች ለመትከል ያቀደው፡፡

 

በውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ቱርክ ቀዳሚ ሆና እንድትቀጥል ኢትዮጵያ ፍላጎት አሳየች

በውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ቱርክ አሁንም ቀዳሚ ሆና እንድትቀጥል ኢትዮጵያ እንደምትፈልግ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አስታወቁ፡፡ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ይህን ያስታወቁት የቱርክ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን ባደረጉላቸው ግብዣ ወደ ቱርክ  ባቀኑበት ወቅት ነው። በወቅቱ  በአንካራ ቤተ መንግስት ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት የሁለትዮሽ ግንኙነቱንና ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለማጠናከር  የሚያግዝ  ነው።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ በጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለመሆን እየሰራች ነው። በዚህም የቱርክ ሚና ጎልቶ እንዲወጣ ትሻለች ብለዋል።«በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ቱርክ አሁንም ቀዳሚ ሆና እንድትቀጥል ኢትዮጵያ ትፈልጋለች፡፡እኛ በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ይፋ አድርገናል፡፡ በዚህ ግንባታ ላይ የቱርክ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች እንዲሳተፋ ጋብዘናል፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የቱርክን ባለሀብቶች ለመቀበል ዝግጁ ናት፡፡ 400 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንም በቱርክ ነፃ የትምህርት ዕድል ማግኘታቸው የግንኙነታችን ማሳያ ነው» በማለት  አሁንም ቱርክ መሰል ድጋፏን እንድታጠናክር ጠይቀዋል።

የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን በበኩላቸው፤ የሁለቱ አገራት የንግድ ልውውጥ መጠን አሁን ካለበት 439 ሚሊዮን ዶላር፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንዲደርስ ቱርክ ትሰራለች ብለዋል፡፡በሃገሪቱ ካሉ የመንግስት ባንኮች ብድር በማመቻቸት የቱርክ  ባለሀብቶችን እንደግፋለን ያሉት ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን ፣ የኢትዮጵያ መንግስትም በተመሳሳይ ለባለሀብቶቹ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ  የአንካራ ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካና በቱርክ መካከል ጠንካራ ግንኙነት እንዲፈጠር ላበረከቱት አስተዋፅኦ ለፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ የክብር ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡ በወቅቱም በዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን በማግኘታቸው መደሰታቸውን  ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ እአአ ከ2006 እስከ 2013 በቆዩባቸው የአምባሳደርነት ዘመናት የአገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸው፤  ግንኙነቱ በትምህርት መስክም ይበልጥ መጠናከር  አለበት ብለዋል።

የቱርክ መንግስት ባለፈው ዓመት በአገሪቱ የተቃጣውን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ለማክሸፍ የተጠቀመበትን ዴሞክራሲያዊ ሂደትም  ፕሬዚዳንቱ አድንቀዋል። የአንካራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ኤርካን ኢቢስ የአንካራ እና የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲዎች በትምህርት፣ በሳይንስ እና በባህል ፕሮግራሞች አብረው መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ገልጸዋል።

DAILY SABAH WITH ANADOLU AGENCY

 

 አየር መንገዱ 159 ሚሊዮን ዶላር ብድር አገኘ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማስፋፋት እቅዱን ለማሳካት ይረዳው ዘንድ ከአፍሪካ ልማት ባንክ የ159 ሚሊዮን ዶላር ብድር ተቀብሏል፡፡ ብድሩ በአፍሪካ ንግድ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ የታገዘ ሲሆን አየር መንገዱ ለሚያደርገው የማስፋፋት እቅዱና በሚቀጥለው ዓመት 140 አውሮፕላኖች እንዲኖሩት ለማድረግ ይጠቀምበታል፡፡ አየር መንገዱ በአፍሪካ በቀዳሚነት ደረጃ የሚገኝ ሲሆን እ.አ.አ. በ2025 የአውሮፕላን ብዛቱን በእጥፍ በመጨመርና ገቢውን ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ አቅዷል፡፡

የአፍሪካ ንግድ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ በኢትዮጵያ የብድር ስምምነት ሲፈጽም ይህ የመጀመሪያው ሲሆን በቀጣይም  በሀገሪቱ የሃይል ዘርፍ ለመሳተፍ ፍላጎት አለው። በነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር የሚገነባው በ400 ሜጋዋት የጸሐይ ሃይል ልማት ፕሮጀክት ላይ ለመስራት ይፈልጋል፡፡ የኤጀንሲው ዋና ስራ አስፈጻሚ ጂኦርጅ ኦቴይኖ የኢትዮጵያ አንጸባራቂ የገበያ አጋጣሚና እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ሀገር በመሆኗ ይሄ ተሳትፎ ከሚቀጥሉ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱና የመጀመሪያው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

The East African

 

የፈረንሳዩ ኩባንያ በኢትዮጵያ ግዙፍ የብቅል ፋብሪካ ሊገነባ ነው

የፈረንሳይ የገብስ ህብረት ስራ ቡድን አክሰሪያል በኢትዮጵያ በቅርቡ ስራ የሚጀምር ግዙፍ የብቅል ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እንደሚገነባ ተገለጸ፡፡

ፋብሪካው አአአ በ2018  መጨረሻ አካባቢ የማምረት ስራውን የሚጀምር ሲሆን በዓመት እስከ 60 ሺ ቶን ብቅል የማምረት አቅም እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡ የቢራ ገበያ በታዳጊ አገራት በተለይ በአፍሪካ በጣም እያደገ መጥቷል። በመሆኑም ኩባንያው በእነዚህ አገራት የብቅል ማምረቻ ፋብሪካ እንደሚከፍትና የአካባቢው ነዋሪዎችንም ገብስ በማምረት ቀጥታ ተጠቃሚ ለማድረግ የረጅም ጊዜ እቅድ አለው።

Reuters

 

ተመራማሪዎች በማርስ ለሚደረግ ጥናት የአፋር ደናክልን ተሞክሮ ለመውሰድ ጥናት እያደረጉ ነው

በዓለም በሙቀቱ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው፣ በልዩ ተፈጥራአዊ ገጽታ ያለው የአፋር ደናክል አካባቢ ከማድሪድና ጣሊያን የተውጣጡ ምሁራን በመቐለ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ጥናታቸውን ያደርጋሉ። ተመራማሪዎቹ በጣም አስቸጋሪ በሆነ ቦታ የአካባቢውን ሙቀት ተቋቁመው ስለሚኖሩ ህይወት ያላቸውን ነገሮች ያጠናሉ። ይህ ከኤርትራ በ100ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ የሚገኝ ልዩ ሙቀታማ  ስፋራ በአማካኝ 34 ነጥብ 4 ዲግሪ ሴሊሲየስ ሙቀትና በዓመት 4 ሚሊ ሜትር ብቻ  የዝናብ መጠን አለው፡፡

ህይወታውያን ጥናት ለማድረግ ህይወት ለምን ያህል  ጊዜ ልዩ በሆኑ ሌሎች ፕላኔቶች( እንደ ማርስ) በመሳሰሉት መቆየት እንደሚችሉ ጥናት በማድረግ በተለይ የአፋር ዳናክል ላይ የሚገኙ ተህዋስያን (ባክቴሪያ) በአስቸጋሪ ሙቀት ያለው አካባቢ፣ አሲድና ጨዋማ ስፍራ እንዴት መኖር እንደሚችሉ ለመረዳት ያስችላል፡፡ ይሄ በደናክል የሚገኝ አዲሱ ግኝት በማርስ ላይ ለሚደረገው ጥናት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው እንዲሁም በማርስ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚችልም ተመራማሪዎቹ ይጠቁማሉ፡፡

Deccan herald, The New York Times

 

ኢትዮጵያ ድርቁን ለመግታት በስፋት እየተንቀሳቀሰች ነው

ከአሜሪካው የግብርና ክፍል የተገኘ መረጃ እንደሚያመላክተው የኢትዮጵያ መንግስት የዓለም አቀፍ ልማት አጋር ድርጅቶች በኢትዮጵያ ምስራቃዊና ደቡባዊ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ለመግታት አስፈላጊውን እርምጃ እያደረገች እንደምትገኝ እአአ በጥር 30 ቀን 2017 የወጣ የግሎባል አግሪካልቸር ኢንፎርሜሽን ኔትዎርክ ሪፖርት አስታውቋል፡፡  በኢትዮጵያ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ህዝቦች አስቸኳይ የምግብና ሌሎች ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የአሜሪካ ግብርና ዲፓርትመንት ጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትና ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች እአአ በጥር 17 ቀን 2017 የሰብአዊ እርዳታ መስፈርት ሰነድ ይፋ ማድረጋቸውንም አስታውሷል።

የሰብአዊ እርዳታ መስፈርት ሰነድም ኢትዮጵያ በተጠቀሱ አካባቢዎች በአሁኑ ሰዓት ያጋጠማትን ድርቅ በመረዳት ድርቁን ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ ለማድረግ ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህም መሰረት 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ህዝብ ለመርዳት የ948 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ለማሰባሰብ ጥሪ አድርጓል፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ጉዳዩ ሳይዘገይ የዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ በአፋጣኝ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  ጥሪ አድርጓል፡፡

Black sea grain

 

የኢትዮጵያ የጎማ ገበያ እአአ በ2022  ብልጫ እንደሚያሳይ ተጠቆመ

በኢትዮጵያ እያደገ ባለው የኮንስትራክሽን ዘርፍ ስራዎች፣ የተሸከርካሪዎች ብዛት መስፋፋትና ፈጣን የጎማ መለዋወጫ ገበያ ምክንያት በ2022 በሀገሪቱ የጎማ ፍላጎት ያደርጋል፡፡ የቴክ ሳይንስ ጥናት ሪፖርት እንደሚ ያመላክተው የኢትዮጵያ የጎማ ገበያ እአአ በ2022 ከ180 ሚሊዮን  ዶላር በላይ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ባለፉት ዓመታት የሀገሪቱ አጠቃላይ ገቢ ከፍተኛ እድገት ያሳየ ሲሆን በሚቀጥሉት ዓመታትም የቁጠባ እድገቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡

     ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የጎማ ገበያው በአዲስ አበባ፣ ሃረሪና ኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አብላጫ የታዩባቸው እንደነበሩና በሚቀጥሉት ዓመታት እአአ እስከ 2022  የገበያው በአብላጫነት የሚመሩት እነዚህ ክልሎች እንደሚሆኑ ጥናቱ ያመላክታል፡፡ በኢትዮጵያ ገበያ ላይ በዋናነት የተቆጣጠሩት ቻይናውያን ሲሆኑ ዋና ዋና የሚባሉ የጎማ ምርቶችን በከፍተኛ ማምረቻ ፋብሪካዎች ሼር በመያዝ እያንቀሳቀሱት ይገኛሉ፡፡

Market Watch

ከሞኒተሪንግ ክፍል

Published in ዓለም አቀፍ

የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት እና ዩኒየኖች ለአርሶአደሩ ከግብአት አቅርቦት እስከ ምርት ግብይት የደረሰ አገልግሎት ይሰጣሉ። በዚህ አገልግሎት ውስጥ  ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አልሆነላቸውም። አገልግሎታቸውን የሚያደናቅፍ ተግዳሮት ፈትኗቸዋል። ለአርሶአደሮች የተለያዩ የግብርና ግብአቶችን ለማቅረብ የአሰራር ችግሮች አጋጥመዋቸዋል። አንዳንዶቹ ግብዓት ገበያው ላይ እንደልብ አለመኖሩን ሲያነሱ ሌሎች ደግሞ የአሰራር ክፍተቶች የግዢ ሂደቱ ላይ አማራጭ እንዳይኖር እክል መፍጠሩን ይናገራሉ።

የአጋርፋ ከጀሞ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ ሱልጣን ሃጂ እንደሚናገሩት፣ዩኒየኑ በባሌ አካባቢ አጋርፋ ወረዳ በ2003 ዓ.ም ስራ ሲጀመር 190 ሺ ብር እና ጥቂት አባላት ብቻ ነበረው። በአሁኑ ወቅት የአባላት ማህበሩ ቁጥር 17  ሲሆን  ካፒታሉንም አራት ሚሊዮን ማድረስ ተችሏል። የተለያዩ የግብርና ግብአቶችን ማለትም የጸረተባይ ኬሚካል፣ ምርጥ ዘር እና የተለያዩ ኬሚካሎችን በዋናነት ከኦሮሚያ ግብርና ህብረት ስራ ማህበራት ፌዴሬሽን ይገዛል። በዘንድሮ ዓመት የጸረ ፈንገስ ኬሚካል 41 ሺ ሊትር ተገዝቶ ዩኒየኑ ለአርሶአደሮች በዝቅተኛ ትርፍ እያቀረበ ይገኛል። እንዲሁም 14 ሺ ሊትር ጸረተባይ መድሃኒት  እያከፋፈለ ነው። የተለያዩ የእንስሳት እና የአትክልት መድሃኒቶች በገበያ ላይ ካለው የሃያ በመቶ ቅናሽ በማድረግ ለማቅረብ ተችሏል።

ይሁንና ግብዓቶቹ በብዛት የማይገኙ በመሆኑ እጥረት ያጋጥማል።አማራጭ አቅርቦት ባለመመቻቸቱም ግብአቱ ከውጭ አገራት ተጓጉዞ እስኪመጣ ድረስ ግብይት አይፈጸምም። በመሆኑም  የእርሻ ምርቱ  ላይ የሚደርሰውን አረም እና ጉዳት መቀነስ አላስቻለም። የፌዴሬሽኑን የግብአት አቅርቦት በማጠናከር አርሶአደሩ የሚፈልጋቸው ኬሚካሎች እና ምርጥ ዘሮች በስፋት ሊቀርቡ እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።

በኦሮሚያ ክልል ከሐሮማያ አካባቢ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን የግዢ ባለሙያ የሆነው ወጣት ከድር ጀማል በበኩሉ፤ ዩኒየኑ በተለይ የአትክልት አምራቾችን በብዛት በማሳተፍ 1ሺ700 የሚጠጉ አርሶአደሮችን በአባልነት መያዙን ይናገራል። ዩኒየኑ ለአንድ አርሶአደር እስከ ሃያ ኪሎ ግራም የሚደርስ የአትክልት ዘር በየዓመቱ ያቀርባል። የመንግስት ምርጥ ዘር አቅርቦትም እንዲሁ ለግብርናው ዘርፍ ትርፋማነት የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት በዩኒየኖች አማካኝነት ለአምራቹ ይከፋፈላል። ለአርሶአደሩ የሚቀርበው አብዛኛው የግብርና ግብዓት ከክልሉ ህብረት ስራ ፌዴሬሽን በመሆኑ ሁሉም ዩኒየኖች የፌዴሬሽኑን በቂ አቅርቦት ይፈልጋሉ። በዚህ ሂደት ደግሞ የግብዓት እጥረትእንደሚያጋጥማቸው ይናገራል።

በተለይ የአትክልት ምርጥ ዘር በወቅቱ እና በብዛት የማይገኝበት እድል ሰፊ ነው። የድንች ጸረ ተባይ የሆነው «ሬዶሚን» የተሰኘው ኬሚካል በአምራቹ ዘንድ በብዛት የሚፈለግ ቢሆንም በቀላሉ የሚገኝ አይደለም። እንዲሁም «ሄለራት» የተባለው ለጥቅል ጎመን አስፈላጊ የሆነ የጸረተባይ መድሃኒት በወቅቱ ባለመቅረቡ ምክንያት አርሶአደሮች ምርታቸው እየተበላሸ በየጊዜው ይማረራሉ። ይህም በመሆኑ በአገራዊ ምርት እድገት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ ከፍተኛ  መሆኑን ነው ያስታወሰው።

እንደ ወጣት ከድር ገለፃ ከሆነ የግብዓት እጥረቱን ለመቅረፍ ብሎም አርሶአደሮቹን ተጠቃሚ ለማድረግ የፌዴሬሽኖችን አቅም ከማጠናከር ባለፈ ከግል አቅራቢዎች ላይ የግብአት ግብይት እንዲፈጸም መፈቀድ ይኖርበታል። በዋናነት ደግሞ ዩኒየኖች እና ማህበራት የግብርና ግብአቶችን ከተመቻቸው የግል አቅራቢዎች እንዲሸምቱ የሚያስችል ቀላል አሰራር ያስፈልጋል። ይህም ሲሆን የግብርናውን ምርት በጥራት እና በብዛት ማምረት ይቻላል። በመሆኑም የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ እንዲሁም የተለያዩ የመንግስት አካላት የግብአት አማራጮች እንዲሰፉ የአሰራር እና የህግ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል።

«የግብዓት እጥረት ለዩኒየኖች እና አርሶአደሮች አስቸጋሪ ሆኖ የዘለቀ ጉዳይ ነው» የሚሉት ደግሞ የራያ ዋርከና የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ መሀመድ የሱፍ ናቸው። ዩኒየኑ በዘጠኝ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት እና በሶስት ሺ684 አባወራዎች አማካኝነት ከ13 ዓመታት በፊት መቋቋሙን ነው የሚናገሩት። ለአርሶአደሩ መሬት የሚውሉ 30ሺ ሊትር የተለያዩ አይነት የጸረተባይ መድሃኒቶችን በየዓመቱ የማቅረብ አቅም አለው። ሆኖም ግን ባለፉት ዓመታት የግብአት በተለይም የጸረተባይ መድሃኒቶች እጥረት አጋጥሞታል።

ዩኒየኑ ከመሰረቱ የአርሶአደሩን ችግር ለመፍታት የተቋቋመ ሲሆን በተለያዩ የግብይት እና እሴት መጨመር ተግባሮች ላይ እየተከናወነ ይገኛል። በግብአት አቅርቦትም የተለያዩ ምርቶች ለአርሶአደሩ በሽያጭ መልክ እንዲያገኝ እየተደረገ ነው። በመንግስት የሚቀርበውም ማዳበሪያ እንዲሁ ለአርሶአአደሩ እንዲደርስ ይደረጋል። ይሁንና የግብአት አቅርቦቱ የአርሶአደሩን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ያሟላ ነው ማለት አይቻልም።  የሚጠየቁ የኬሚካል ግብአቶች በሚፈለገው መጠን በአቅራቢያቸው ባለመገኘታቸው መቸገራቸውን ይናገራሉ።

ከኦሮሚያ ግብርና ህብረት ስራ ማህበራት ፌዴሬሽን በኩል የማይገኙ የግብርና ግብአቶች በተለይም ኬሚካሎችን ለመግዛት ሲታሰብ በመጀመሪያ ከክልሉ ፍቃድ ማግኘት ይጠበቃል። ይህ አሰራር ደግሞ የጊዜ ሂደቱን ያራዝመዋል። በዚህ መንገድ ዩኒየኑ እስከአሁን ድረስ ከግል አቅራቢዎች የገዛው ግብአት የለም። በመሆኑም ግብአቶቹን በአቅራቢያ የሚያገኝበት አማራጭ መጠናከር እንደሚኖርበት ነው ያሳሰቡት።

የፌደራል ኅብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር የግብርና ግብአቶች አቅርቦትና ፍላጎት መመጣጠን እንዳለባቸው ይገልጻሉ። በግብርና ግብአት አቅርቦት ላይ የሚነሳው የፌዴሬሽኖች አቅም ይጠናከር የሚለው ጥያቄ ተገቢ በመሆኑ በየጊዜው እየተሰራበት ይገኛል። ግብአቶች በወቅቱ እና በስፋት ለአርሶአደሩ እንዳይቀርቡ የመሬት እና የፋይናንስ እጥረት አለ። ይህንን እና መሰል ችግሮችን በአካባቢው ያሉ አስፈጻሚ አካላት በቂ ትኩረት ባለመስጠታቸው ችግሩ ይባባሳል። ይህን ለመፍታትም ከሚመለከታቸው አመራሮች ጋር የጋራ ውይይት በየጊዜው እየተደረገ  መሆኑን ነው ያስታወሱት። «ይሁንና ከመንግስት ወይም ከፌዴሬሽኖች በተጨማሪ ከግል አቅራቢዎች ግብአቶችን መግዛት የሚከለክል አሰራር የለም» ይላሉ።

መንግስት የሚከተለው የነጻ ገበያ ስርዓት በመሆኑም ማንኛውም አቅራቢ መሳተፍ ይችላል፤ ዩኒየኖችም መግዛት ይችላሉ። ለማስታወስ ያህል ከ15 እና 20ዓመታት በፊት በአገሪቷ ውስጥ ከ15 በላይ የግብርና ግብአት አቅራቢ የግል ተቋማት ነበሩ። አብዛኞቹ በገበያው የውድድር ሜዳ ውስጥ መፎካከር ስላቃታቸው ገበያውን ጥለው መውጣታቸውን ይናገራሉ። አሁን ላይ የቀሩት የግል አቅራቢዎች በጣት የሚቆጠሩ ሲሆን፤ ከውድድር ውጭ የነበሩት ራሳቸውን እያጠናከሩ ወደቀድሞ ስራቸው ለመመለስ እየሞከሩ ናቸው።

በዚህ ረገድ ዩኒየኖች ከግል አቅራቢዎች እንዳይረከቡ የሚያዝ ምንም አይነት ክልከላ የለም። ይሁንና ማዳበሪያ ከውጭ አገር በሚመጣበት ወቅት ሁሉም ዩኒየኖች አስመጪ ከሆኑ ወጪ ቆጣቢ አይሆንም በሚል መንግስት እያስገባ ይገኛል። ይህም የማዳበሪያው ዋጋ ላይ ጭማሪ በማስከተል አርሶአደሩን ተጎጂ እንዳይሆን ከመከላከል የመነጨ አሰራር ነው። እያንዳንዷ ተጨማሪ ሳንቲም መጨረሻ ላይ የግብአቱ ተጠቃሚ የሆነው አርሶአደር ኪስ ላይ ጫና  ያሳድራል። በመሆኑም ማዳበሪያ  በተደራጀ መንገድ ወደ አገር ውስጥ እየገባ ይገኛል።

ይህም የተማከለ አሰራርን በመከተልና የትራንስፖርት ወጪን ለመቀነስ ይረዳል። ምርጥ ዘር በተመለከተ የሚባዛው እና የሚሰራጨው በህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ነው። ይሁንና እዚህም ላይ የግል ባለሃብቱ ቢሳተፍ ያዋጣዋል። የህብረት ስራ ማህበራትም ቀጥታ ግብይት በመፈጸም ሊጠቀሙበት ይችላል። በመሆኑም በማህበራቱ በኩል ከግሉ ዘርፍ አዋጪ ዋጋ እና ጥራት ካገኙ የአርሶአደሩን ምርት ለማሳደግ ግብይት መፈጸም ይችላሉ። ይህም ዘርፉን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል።

የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአሁኑ ወቅት ከ79 ሺ በላይ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት፣ 373 የህብረት ስራ ዩኒየኖች እና አራት የህብረት ስራ ፌዴሬሽኖች በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። በስራቸውም 15 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚደርሱ አባላትን ያፈሩ ሲሆን፤ ከጊዜ ወደጊዜም የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች እያቃለሉ ይገኛል።

ጌትነት ተስፋማርያም

Published in ኢኮኖሚ

ከትናንት እስከ ዛሬ ድረስ በማህበራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊ  እና ሌሎች ጉዳዮች ብሎም ስለ ሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ እና በቀጣይ መደረግ ስላለበት የመፍትሄ አቅጣጫ ከቀድሞ የአገሪቱ ርዕሰ ብሄር ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ!

አዲስ ዘመን፡- በሕገ መግስቱ ሦስተኛው ገፅ ላይ የእርስዎ ስም ይነበባል፡፡ ይህን ሲያዩት ምን ይሰማዎታል?

ዶክተር ነጋሶ ፡- የህገ መንግስቱ ጉዳይ ሲነሳ ከማርቀቅ ጀምሮ በጉባዔ አስኪፀድቅ ድረስ ተሳትፌያለሁ፡፡ የአርቃቂ ኮሚሽን አባል ነበርኩኝ፡፡ ያኔ የሽግግር መንግስት ወቅት ነበር፡፡ በማርቀቁ ረገድ የተወካዮች ምክር ቤት፣ ከፓርላማ ውጭ ከሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሁም ከማህበራት ጋር ነው የተረቀቀው፡፡ ከሽግግር መንግስቱ ተወካይ በፓርላማ ሰባት ሰዎች ብቻ ነበርን፡፡ 29 ሰዎች በአርቃቂ ኮሚሽን ውስጥ ነበሩበት፡፡ ከውጭ ፓርቲ በጉዳዩ ላይ ለመሳተፍ በጋዜጣና ሬዲዮ ጥሪ ተደርጎ ፈቃደኛ የሆኑ ሰባት ፓርቲዎች ተሳትፈዋል፡፡ የንግድ ምክር ቤት፣ የሴቶች፣ የማህበራት፣ የሃይማኖት አባቶችም እንዲሁ በሂደቱ ተሳትፈዋል ፡፡

 ከኢህአዴግ አባላት ሆነው ግን በኢህአዴግ ስም ሳይሆን  ግለሰብ ደረጃ የተሳተፍነው አቶ ዳዊት ዮሐንስ እና (ኢህዴን) እና ከ(ኦህዴድ) እኔ ነበርኩ፡፡ ከሁለቱ የኢህአዴግ አባላት (ህወሃት) እና (ደህዴን) ማንም አልነበረም፡፡ ለማንኛውም ህገ መግስቱ ከተረቀቀ በኋላ ወደ ሽግግር ተወካዮች ምክር ቤት ከተወያየ በኋላ ወደ ጉባኤ ተላለፈ፡፡ ስድስት ሳምንት ተመክሮበታል፡፡ በዚህ ጊዜ እኔ ሊቀመንበር፣ አዲሱ ለገሰ ምክትል ሊቀመንበር እንዲሁም አባተ ኪሾ ፀሀፊ ነበርን፡፡ በርካታ የኮሚቴ መሪዎችም ነበሩ፡፡ ትልቅ ስራ ነው የሰራነው፡፡ በጣም ከልቤ የተሳተፍኩበት ነው፡፡ አንዳንድ ድክመቶችና እና ችግሮች ቢኖሩበትም ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ነው ያፀደቅነው፡፡ የህገ መንግስቱ ጉዳይ ሲነሳ ኩራት እና ደስታ ነው የሚሰማኝ፡፡ ትዝታውም አብሮ ይመጣል፡፡ በእርግጥ ማንሳት የምፈልገው ነገር ብዙ ሰዎች ይሳሳታሉ፡፡ ‹‹ይህ ህገ መንግስት የኢህአዴግ ነው››ይላሉ፡፡ ይህ ስህተት በመሆኑ መታረም አለበት፡፡  ፈርሜበታለሁና  ኩራት ይሰማኛል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ህገ መንግስቱ ሲጠነሰስ እርስዎ ነበሩ፡፡ እርስዎ አሁን 73 ዓመት ሆኖዎታል፡፡ ስለ ህገ መንግስቱ ዛሬ ላይ ሆነው ሲያስቡት  ምን ይላሉ?

ዶክተር ነጋሶ፡- ሕገ መንግስቱ ሀገሪቱ የምትተዳደርበት የበላይ ህግ ነው፡፡ በግለሰብ፣ በማህበረሰብ፣ በህዝብና መንግስት መካከል የተደረገ የጋራ ውል ነው፡፡ ለአንድ ሀገር ህልውና እና ህዝብ ጥቅም መዋል አለበት፡፡ ይዘቱም ለሀገር ጥቅም እስከሆነ ድረስ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ላይ የተመሰረተና ከጊዜው ጋርም መጣጣም አለበት፡፡ የህግ የበላይነትም ሊከበር ይገባል፡፡ በህገ መንግስቱ የሚመሰረት መንግስትም ተቀባይነት ሊኖረው ይገባል፡፡

በብዙዎቻችን ዘንድ ህገ መንግስቱ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል እንላለን፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ምክንያቶች ተቀባይነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ ህግ መንግስቱን ከማርቀቁ እስከ ማፅደቁ ባለው ሂደት ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶችና የህብረተሰብ ክፍል አሳታፊነት ላይ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በወቅቱ አንዳንድ ተቀባይነት የነበራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አልተሳተፉበትም፡፡ ኦነግ እና አንዳንድ የኦሮሞ ድርጅቶች ፣ ኢህአፓ፣ ኢሰፓ፣ ሚኤሶን በወቅቱ ብዙ ተቀባይነት ያላቸው ሆነው አልተሳተፉም፡፡ ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት እነዚህ ድርጅቶች በውል ባይኖሩም አባሎቻቸው እና አመራሮቻቸው እንዲሁም ደጋፊዎቻቸው ህገ መንግስቱ ‹‹የኢህአዴግ እንጂ የእኛ አይለም›› በሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በወቅቱ ከተሳታፊነት አኳያ ያደረግነው 73 ጥያቄዎች አዘጋጅተን ለ23ሺህ ቀበሌዎች በምርጫ መልክ ጥያቄ በትነን መልስ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ በተፈለገው መጠን ፓርቲዎች አልተሳተፉም፡፡  ህዝበ ውሳኔ ቢደረግ መልካም ነበር፡፡ ይህ አልተደረገም፡፡

በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡ ግን እስካሁንም ድረስ ተቀባይነት ያላገኙ በርካቶች ናቸው፡፡ ለአብነት አናሳዎች በተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆን አለባቸው ይላል፡፡ ይህ አለ? የኦሮሚያ እና አዲስ አበባን ግንኙነት በተመለከተ እስከአሁን ህግ አልወጣም፡፡ በእኔ እይታ ደግሞ አንቀፅ 29፣ 30፣ 31፣ 38 ህገ መንግስቱ ባስቀመጠው መሰረት ተግባራዊ አልሆኑም፡፡

ከ22 ዓመት በፊት ህገ መንግስቱ ሲፀድቅ የነበረው እና በወቅቱ ያልተገነዘብነው የምርጫ ስርዓትም ሊፈተሸ ይገባል፡፡ በአንድ ቀበሌ አብላጫ ድምፅ ያገኘ ሰው ይመረጣል፡፡ ከዚያም 547 ሰው ፓርላማ ይገባል፡፡ አሸናፊ ሁሉን ነገር ያጠቃልላል፡፡ ይህ ስርዓት ትክክል ነበር ወይ? የሚለው ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ስለዚህ የዜጎችን ድምጽ እኩል ለመስማት ያስችላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይህ በርካታ ብሄርና ብሄረሰቦች ባሉበት ሲታይ ድክመት ነው፡፡ በክልልም ሆነ በፌደራል ምክርቤቶች አሸናፊ ናቸው የሚቀመጡት፡፡ ስለዚህ የህገ መንግስት ክርክር በሚነሳበት ወቅት የሚወስነው አንድ ፓርቲ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህም ኢህአዴግ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ሌላም ፓርቲ ዕድሉን ካገኘ በዚሁ ነው የሚመራው፡፡ ስለዚህ ይህን የሚመራ ነፃ ፍርድ ቤት እንዲኖር ብንከራከር ጥሩ ነበር፡፡ በወቅቱ አላሰብንበትም፡፡

አዲስ ዘመን፡-  የተማሩ ሰዎች ያከተተ ብቻ ነበር ማለት ነው፡፡ ሁሉም ከዳር ዳር ተሳትፈዋል? ርቀት ቦታ ላይ ያሉትስ ተሳታፊ ነበሩ?

ዶክተር ነጋሶ፡- ጥያቄውን ይዘው የሄዱት አወያዮች ለህዝቡ በደንብ ይገልፃሉ፡፡ የእኛ ህዝብ ብዙ ሰዎች እንደሚሉት አይደለም፡፡ የተማረ ባይሆንም ስለ መብቱ ያውቃል፡፡ ከህዝቡ ንቃተ ህሊና አኳያ መብቱን አሳልፎ አይሰጥም፡፡ በወቅቱ ለማወያየት የሄዱት ከብሄር ብሄረሰብ ተወከለው ነበር፡፡ እንደ ሪፖርቱ ከሆነ  23ሺህ ቀበሌዎች ተሳትፈውበታል። ግን ያን ጊዜ ስንት ቀበሌዎች እንደነበሩ አላውቅም። በሁሉም ቀበሌዎች ተዳርሷል ወይስ አልተዳረሰም የሚለውን ምናልባት ይሄ ቴክኒካል ጉዳይ ነው፡፡ የትራንስፖርት ችግር አለ፤ ሄደው የሚያወያዩ ሰዎች ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ተጠርተው፤ ስልጠና ተሰጥቷቸው አማርኛ ይሰማሉ ወይ? የሚለው ታይቷል፡፡ የእኔ ጥያቄ አብዛኛው ህዝብ አልተሳተፈበትም። መጨረሻም ላይ ከጸደቀ በኋላ ይሄ የጸደቀው ህገ መንግስት እናንተን ይወክላል፤ አይወክልም? ተብሎ ተጠይቆ ይወክለናል ብሎ ህዝበ ውሳኔ አልተሰጠበትም የሚል ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የፌዴሬሽን ምክርቤት የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የሚወከሉበትና የተለያየ አስተሳሰብ  የሚራመድበት ይሆናል ተብሎ ይታሰባል ስለሆነም ጫና መፍጠር አይችሉም ነበር?

ዶክተር ነጋሶ፡- ልክ ነህ፡፡ ግን እዚህ የሚገቡት ከየትኛው ፓርቲ ነው? ዴሞክራሲያዊ፣ አሳታፊና ተመጣጣኝ ድምፅ ቢኖር መልካም ነበር፡፡ ግን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ቢወከሉም የተለየ ሃሳብ የማራመድ እድል የላቸውም፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአንድ ስርዓት ውስጥ ቢሆኑስ የተለያየ አስተሳሰብ ለማራመድ ህገ መንግስቱ ይከለክላልን?

ዶክተር ነጋሶ፡- ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ድርጅታዊ አሰራር የለም፡፡  ከፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ወደ አባል ከወረደ በኋላ ማፈንገጥ አይቻልም፡፡ የፓርላማ አባላት የፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ ከፓርቲው አፈንግጦ ምንም ማምጣት አይችሉም፡፡ ከፓርቲው ካፈነገጡ ይገመገማሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ ርዕሰ ብሔር የነበሩትና አብዛናው ህዝብ ተሳትፏል ብለው የፈረሙት እርስዎ ነዎት፤ ይህ ነገር እርስ በእርሱ አይቀራንም?

ዶክተር ነጋሶ፡- ከዚህ በፊትም ተናግሬያለሁ፡፡ ሁሉም ህዝብ ተሳትፎበታል፤ ስኬታማም ነበር ብዬ መናገሬ ስህተት ነው፡፡ ህዝቡን ይቅርታ ጠይቄያለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ህገመንግስቱ ዛሬ ላይ ምን መሆን አለበት ይላሉ?

ዶክተር ነጋሶ፡- መጀመሪያ ላይ የጠቀስኳቸው ጥያቄ የሚነሳባቸው ያልተተገበሩ ድክመቶች አሉ። እነዚህ አንቀጾች እንደገና አሳታፊ የሆኑ መድረኮች ተከፍተው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ የማሻሻያ አንቀጾች ተዘጋጅተውና ገብተውበት፤ ተቀባይነት አላቸው ወይስ የላቸውም? ተብሎ ህዝቡ ተጠይቆ  ህገ መንግስቱን ማሻሻል ይገባል፡፡ ህገ መንግስቱ አይሻሻልም የሚሉትንም ሆነ የእኛ አይደለም የሚሉት ትክክል አይደሉም።

በሌላ መንገድ ደግሞ ህገ መንግስቶች በየጊዜው እየተሻሻሉ የሚሄዱ ናቸው እንጂ፤  እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቁጭ ብለው የሚቀሩ አይደለም። አዲስ መንግስት እየተመሰረተ ሌላ አዲስ ህገ መንግስት የሚወጣበት አካሄድ ትክክል አይደለም፡፡ በየጊዜው እየተሻሻለ መሄድ አለበት ብዬ ነው የምገምተው። ለአብነት አንቀፅ 39 ተግባራዊ አልሆነም፡፡

አዲስ ዘመን፡-  ከላይ የተጠቀሷቸው ፓርቲዎችን መንግስት ተዳክመዋል ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅት የጎላ ተፅዕኖ መፍጠር ይችላሉ ብለው ያስባሉ?

ዶክተር ነጋሶ፡- እነርሱ የሚፅፉትን እና የሚናገሩትን እየተከታተልኩ አይደለም፡፡ ግን ጥያቄዎች እየተነሱ አይደለም? እነዚህ ፓርቲዎች በወቅቱ ነበሩ፡፡ በህዝቡ ውስጥ ደጋፊዎች ነበሯቸው፡፡ ከዚያም በሂደት እንዲዳከሙ አልተደረገምን? በዚህ 25 ዓመት ውስጥ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሲንቀሳቀሱ እና ሲደራጁ ምን ዓይነት እርምጃ በፓርቲዎች ላይ እንደሚወሰድም አይተናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለ አንቀፅ 39 ገዢው ፓርቲ ጥያቄ አልቀረበም እንጂ ተገቢ ከሆነ እውቅና እሰጣለሁ ይላል? የእርስዎ መከራከሪያ ነጥብ ምንድን ነው?

ዶክተር ነጋሶ፡- የእኔ ሃሳብ አሁንም በተለይ ከአንቀጽ 29 እና 31 ጋር ነው የሚያያዘው። የአመለካካት፣ የሃሳብ ነጻነት መኖር አለበት፤ መከበር አለበት። የተለያዩ ሃሳቦችን የሚይዙ፤ የተለያየም አይነት ሃሳብ ያላቸው ሰዎች በያዙት አመለካከታቸውና እምነታቸው የመደራጀት መብት ሊኖራቸው ይገባል። ይህ ከሆነ በተለያዩ ምክንያቶች «እኔ መገንጠል እፈልጋለሁ» የሚል ግለሰብ ካለ ሀሳቡን በነጻ መግለጽ አለበት ብዬ ነው የምገምተው። ሃሳቡን በነጻነት ገልፆ ያንን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ መደራጀት መብቱ ነው። ያንን የሚደራጅበትን ዓላማ የሚደግፉ ሰዎችን አሰባስቦ ማስተማር የራሱ መብት ነው። ስለዚህ በአንቀጽ 39 መሰረት ያለገደብ እስከ መገንጠል መብት ከተከበረ በዚያ የመገንጠል ሀሳብ ያላቸው ሰዎች መደራጀት መብታቸው ነው። መገንጠል የለብንም ብለው የሚያምኑ ሰዎች ደግሞ እንደዚሁ የመንቀሳቀስና የመደራጀት መብት ሊኖራቸው ይገባል። የለም ጥያቄው የብሔር ጥያቄ ነው የመገንጠልና ያለመገንጠል ጥያቄ ብቻ አይደለም፤ በፌዴራላዊ ስርዓት መተዳደር አለብን የሚሉ ሰዎችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በኮንፌዴሬሽን ነው የምንተዳደረው የሚሉ ሰዎች ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎች ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ እና የመደራጀት መብታቸው መከበር አለበት። ይሄ በትክክል ተግባራዊ ሆኗል ወይ? መብታቸው ተከብሯል ወይስ አልተከበረም? አንድ ጥያቄ ነው።

ስለዚህ እኔ አንቀጽ 39 ተግባራዊ አልሆነም ብዬ የማስብበት ምክንያት አለኝ፡፡ በእርግጥ መገንጠልን በጣም ነው የምቃወመው፡፡ ግን ሁለት ጉዳዮች አሉ፡፡ አንደኛ የነጻነት ጉዳይ ነው፡፡ የአመለካከት፣ የመደራጀት ነጻነቶች እና በዚያም ላይ ተመስርቶ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድበት ሁኔታ ተመቻችቷል ወይ? ከሚለው አኳያ ነው። እነዚህ ሁለቱ ተግባራዊ አልሆኑም። ህዝበ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች ተደራጅተው ሃሳባቸውን ከገለጹ በኋላ ህዝበ ውሳኔ እንዲሰጡ ሁኔታው አልተመቻቸም።

ለምሳሌ ‹‹ኦነግ›› እኔ መገንጠል እፈልጋለሁ ይላል፤ የድሮው፤ የአሁኑን አላውቅም። ካልሆነ በመሣሪያ ኃይል ነው ተግባራዊ የማደርገው ይላል። ህዝቡ ይደግፋል ወይስ አይደግፍም የሚለው በምንድን ነው የሚታወቀው? ኢህአዴግ ኦነግ የሚለው ትክክል አይደለም፤ እኔ የምለው ነው ትክክለኛ ይላል፡፡ ክልሎች ተቋቁመዋል ቋንቋ፤ ተከብሯል ይሄ ይበቃል ይላል። ህዝቡ ራሱ የፈለገውን እየመረጠ ነው፤ ራሱን እያስተዳደረ ነው ይባላል፡፡ የትኛው ፓርቲ ነው በትክክለኛው መንገድ እነዚህ የተለያዩ ሀሳቦችን እየያዘ እየተወዳደረ ወደ ምርጫ የገባው? በምንድን ነው የምናውቀው?

አዲስ ዘመን፡- የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባልም ሆነው ነበር፡፡ ለአብነት የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ አንዱ ነበር፡፡ ለምን እራስዎን አገለሉ?

ዶክተር ነጋሶ፡- ከፖለቲካ ፓርቲ ራሴን ያገለልኩበት በፕሮግራማቸው ያለመስማማት ነበር። ወደ ፓርቲው በምገባበት ጊዜ የውይይት መድረክ ነው እንጂ ፓርቲ አልነበረም። ከዚያ የውይይት መድረኩ ወደ ምርጫ ቦርድ ሄዶ መመዝገብ ነበረበት እንደ ጥምረት። በወቅቱ ወደ ስድስት ፓርቲዎች ነበሩ። በውይይቱ ላይ ሁለት ሰዎች ነበርን እኔና ስዬ አብርሃ። እኛ የድርጅቶቹ አባላት ሳንሆን በውይይት እንሳተፍ ነበር። መድረኩ ወደ ምርጫ ቦርድ ሲመዘገብ አንዱን መምረጥ ነበረብን። ምክንያቱም እንደ ግለሰብ አባል መሆን አንችልም። ስለዚህ የትኛው ውስጥ ብገባ ይሻለኛል? ብሎ መምረጥ ነበረብኝ። አረና ትግራይ የትግራይ ሰዎች ፓርቲ ነው። እኔ ደግሞ የትግራይ አይደለሁም። የደቡብ ህብረትም ነበር። እኔ ግን ደቡብ አልነበርኩም። የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረንስ (ኦብኮ) ነበር። ከእሱም ጋር የኦሮሞም ቢሆን በአስተሳሰብ በተለይም በሶሻል ኢኮኖሚና በብሔር ጥያቄ ላይ ልዩነት ነበረን። እኔ የምደግፈው ብሔር ብሔረሰቦች እስከመገንጠል አንቀፅ 39 በትክክል ተግባራዊ እንዲሆን ነው። የኦፌዴን እና የኦብኮ የሁለቱ ድርጅቶች አንቀፅ 39 ላይ ያላቸው አቋም ከእኔ ጋር የሚስማማ አልነበረም። አንቀፅ 39 እንዲከበር ይህም የሚከበረው የህዝብ ውሳኔ መሰረት ተደርጎ ነው። እነርሱ እዚህ ላይ ጥያቄዎች ነበራቸው አልተስማሙም።

ሌላው የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ነው። አንድነት ደግሞ አንቀፅ 39 በሙሉ ይቃወማል። ስማቸውን መጥቀስ የማልፈልገው ሁለት ሰዎች እዚህ መጥተው «እባክህን የአንድነት ፓርቲ አባል ሁን» ብለው ጠየቁኝ። እነዚህም የኢትዮጵያ አንድነት እንጂ አንቀፅ 39 እንቃወማለን የሚሉ ናቸው። የእናንተን ፓርቲ መቀላቀል አልችልም አልኳቸው። እነርሱም በጣም ታስፈልገናለህ እባክህ አባል ሁነን አሉኝ። ይሄማ ከሆነ ፕሮግራማችሁን ማሻሻል አለባችሁ ስለዚህ አሻሽላችሁ አምጡ ብላቸው «አንተ የምትፈልገውን አንቀፅ ፅፈህ አምጣልን፤  ጉባዔውን እንዳካሄድን እዛ ውስጥ አስገብተን እናፀድቃለን» አሉ። እሺ አልኩና አንቀፅ 39ን በቀጥታ አልጠቀስኩም። የእነሱ አንቀፅ ሶስት አንድ አምስት ነው የምትባለው።

የፃፍኩት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጥያቄዎች የሚፈቱት በዴሞክራሲ መንገድ በውይይትና በድርድር ነው። በዚህ ዓይነት መንገድ ተቀባይነት ካላገኘ ጥያቄው ወደ ህዝብ ይወርድና ህዝብ ይወስንበታል የሚል አስቀመጥኩ። አንቀፅ 39 አላልኩም። የህዝብ የፖለቲካ ጥያቄዎች ብዙ ናቸው። ስለዚህ ሁሉም የፖለቲካ ጥያቄዎች በዚህ ዓይነት በዴሞክራሲ መንገድ በውይይትና በድርድር ካልተፈቱ ወደ ህዝብ ይወርዱና በህዝቡ ውሳኔ ይፈታሉ በሚል አስቀመጥኩና ሰጠሁ።

በፕሮግራም አስገብተው በጉባዔ አፀደቁት። ያን ጊዜ እሺ አልኩና ወደ ፓርቲው ገባሁ። ምክያቱም በእኔ እምነት ፖለቲካ በሃይል አይፈታም በውይይት እንጂ፡፡ አብረን በጥሩ ሁኔታ እየሰራን እያለ ታህሳስ 2006ዓ.ም ጉባዔ አካሄድን፡፡ ለጉባኤው ከሚነሱ ሃሳቦች አንዱ አንቀፅ ሶስት አምስት አንድ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በምን አይነት መንገድ ነው ብዬ ጠየቅሁ፡፡ ማሻሻያው «ሁሉም የፖለቲካ ጥያቄዎች የኢትዮጵያን አንድነት እና ሉዓላዊነት ከተመለከተ በስተቀር» የሚል ሐረግ ገባ፡፡ በዚህ መሻሻል አለበት ተባለ፡፡ ይህ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት ይጨፈልቃል ብዬ ተከራከርኩ፡፡ ወደ ጉባዔ ቀርቦ ፀደቀ፡፡ በማግስቱ ከማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ሲካሄድ ንግግር አደረኩ እና እኔ አልስማም ብዬ ወጣሁ፡፡ በመሃል ሌላ ችግር ተፈጥሮ ፓርቲው አራት ቦታ ላይ ተካፈለ መሰለኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ለመዳከሙ  የእርስዎ እጅ አለበት ይባላል፡፡ ምን ይላሉ? ከፖለቲካ ውጭ ከሆኑስ በቀጣይስ እንዴት ነው ሀገሪቱን ለማገልገል ያቀዱት?

ዶክተር ነጋሶ፡- አንድ ግለሰብ ከፓርቲ በላይ ምን ያክል አቅም አለው፡፡ ሌላ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ይህን ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ እውነታው ግን እኔ በዚህ ጉዳይ ውስጥ እጄ የለበትም፡፡ አሁን ማገልገል የምፈልገው ለተለያዩ የህትመትና ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን አውታሮች ሃሳቤን በመግለፅ ለማስተማር እሞክራለሁ፡፡ የፓርቲ አባል ባልሆንም ከተጋበዝኩ ለማዳመጥ እሄዳለሁ፡፡ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ላይም እሳተፋለሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ ውይይቶች ላይ ሲጋብዙኝ እሳተፋለሁ ሃሳቤንም እሰጣለሁ፡፡ ከአሁን በኋላ የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን አልፈልግም፡፡ የሚስማማኝ ፓርቲ የለም፡፡ ቢኖርም በእድሜና በጤና ጉዳይ አልሳተፍም፡፡

አዲስ ዘመን፡-  የጋራ ሰነድ የሆነውን ህገመንግስት ከማርቀቅ ጀምሮ ሌሎች ለሰሯቸው ተግባራት ተገቢ ጥቅም እና ክብር አግኝተው ይሆን?

ዶክተር ነጋሶ፡- ታሪኩን ታውቀዋለህ መሰለኝ፡፡ ትፅፈዋለህ ወይስ አትፅፈውም? ብትጽፈው ደስ ይለኛል፡፡ አሁን ካለሁበት ቤት ውጣ ተብዬ ሁለቴ ተፅፏል፡፡ ለቤት ውስጥ እና ለኑሮ የማወጣውን ገንዘብ ተከልክያለሁ፡፡ የምኖረው በ1ሺህ 700 ብር የፓርላማ ደመወዝ ነው፡፡ መኪናም ተቀምቻለሁ፡፡ ይህን የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ቢያውቁት ጥሩ ነው፡፡ የቤት ሠራተኛ ባለቤቴ ናት የቀጠረችው፡፡ ጥበቃም በትንሽ ገንዘብ ቀጥሬ ነው። ለህክምና የባለቤቴ ጓደኞች መደሃኒት ገዝተው ባይልኩልኝ  ከባድ ነበር የሚሆንብኝ፡፡ ጠዋት እና ማታ አምስት ኪኒን ነው የምወስደው፡፡ የደም ስሮቼ ይዘጋጋሉ፡፡ ለህክምና እና ምርምራ ከሄድኩኝ ሁለት ዓመት ሞልቶኛል፡፡ የስኳር እና የልብ በሽታ አለብኝ፡፡ ለመመርመር እና ውድ መደሃኒቶች ለመግዛት ገንዘብ የለኝም፡፡ ባለፈው ሳምንት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ፕሬዚዳንቱ ጋር በታክሲ ነው የሄድኩት፡፡  የአገሪቱ አቅም በሚፈቅደው መጠን ክብር እና ጥቅም ይገባኝ ነበር። ይህ ለእኔ ተከልክሏል፡፡ ጥሩ ባለቤት እና የሰው ፍቅር ስላለኝ ደስ ይለኛል፡፡ ግን ይህ አገር እና መንግስት የሚገባኝን ጥቅምና ክብር አልሰጠኝም፡፡ ለወደፊትም ይህን ታሪክ ይፈርደዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለምን እንዲህ ሊሆን ቻለ?

ዶከተር ነጋሶ፡- ወገንተኛ ሆነሃል ተብዬ ነው፡፡ እውነቱን ከተናገርን እኔ የ1997 ዓ.ም ምርጫ በግል ነው የተሳተፍኩት፡፡ በግል ተሳትፌ ፓርላማ ከገባሁ በኋላም በምን ጉዳይ ላይ ወገንተኛ እንደሆንኩ መረጃ የለም፡፡ አዋጅ 255/94 አንቀፅ 7 ጥሷል ነው የተባልኩት፡፡ በአንቀፅ 13 መሰረትም መቀጣት አለበት ተባለ፡፡ ፍርድ ቤት እስከ ሰበር ሰሚ ድረስ ሄጄ ፍርድ በትክክል አልተሰጠኝም፡፡ ግን የመጀመሪያው ፍርድ ቤትም በግል በምርጫ መሳተፉ ችግር የለውም ብሏል፡፡ «ርዕሰ ብሄሩ ለህገ መንግስቱ፣ ለአገሪቱ እና ለህሊናው ታማኝ መሆን አለበት» ይላል ህገ መንግስቱ፡፡ ይህ እያለ ነው ኢ- ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ጥቅማ ጥቅም የተከለከልኩት፡፡ አሁን ካለሁበትም ቤት በማንኛውም ሰዓት በፖሊስ ያስወጡኛል ብዬ ነው በፍርሃት የምኖረው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ከአንድነት ብቻ ሳይሆን ከኢህአዴግም ተለያይተዋል፡፡  እንዴት ተለያዩ?

 ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፡- በመሰረቱ ፍትሃዊ የስልጣን ክፍፍል እና የሃብት ክፍፍል ተፈጥሮ ሰፊው ህዝብ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ የሚፈጠረው በእውነተኛ ሶሻሊዝም ነው፡፡ እስካሁን በዓለም ይህ የተፈጠረበት አላየሁም፡፡ የሩሲያ እና የቻይና ፍልስፍናም በሚለው መንገድ እንዲፈጠር አላዳረጉም፡፡ እኔ ግን እውነተኛ ሶሻሊዝም ተፈጥሮ ፍትሃዊ የስልጣን እና ሃብት ክፍፍል እንዲኖረ ነው የምፈልገው፡፡ ዛሬም እምነቴ ይህ ነው፡፡

እኔ ኢህአዴግን ስቀላቀል «አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው የምንከተለው» ነበር የተባለው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሶሻሊዝም እንደርሳለን የሚል ነበር አስተሳሰቡ፡፡ በዚህ እምነት ነው የገባሁበት፡፡ ለዚህ ዓላማም ብዙ ሺህ ታጋዮች ተሰውተዋል፡፡ ግን በ1993ዓ.ም ላይ ተሃድሶ ተባለ፡፡ የዱሮው ቀርቶ ወደ ካፒታሊዝም ነው የምናመራው ተባለ፡፡ የሶሻሊዝም ነገር አይነሳም፡፡ ይህ መቼ እንደሚሆን አናውቅም ተብሎ ተነገረ፡፡ ያኔ ተሃድሶ ስብሰባው ላይ ጭቅጭቅ ተነሳ፡፡ ግን ይህ 1983ዓ.ም ጀምሮ እየተሠራበት ነበር፡፡ እስከዚህ ድረስ ምንም መረጃው አልነበረኝም፡፡ በወቅቱ የጦፈ ክርክር ነበር፡፡ እኔ ደግሞ የቄስ ልጅ ስለሆንኩ ውሸት አልወድም፡፡ ሌላው እኔ ታጋይ እንጂ ዲፕሎማት አይደለሁም፡፡ በዚህ ላይ ጉዳዩ ሚስጥር ተደርጎ በመያዙ የሃሳብ ልዩነት ተፈጠረ፡፡ በአንድም በሌላም የህዝቡ ጥያቄ አልተመለሰም የሚል እምነት አደረብኝ፡፡ ከዚህ ፓርቲውን ትቼ ወጣሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋርም በሐሳብ አለመግባትም ነበር ይባላል፡፡ እውነት ነው?

ዶክተር ነጋሶ፡- እኔ አቶ መለስን አድነቃለሁ፤ ሳደንቅም ነበር፡፡ የመከራከርና የመናገር አቅም አለው፡፡ በዚህ ላይ ችግር የለብኝም፡፡ በህውሃት መካከል በነበረው 1992 እና 1993 ዓ.ም ክፍፍል በነበረበት ወቅት አፈታቱ ላይ ነው የተለያየነው፡፡ መለስ እና ግብረ አበሮቻቸው የሄዱበት መንገድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የህወሃት አመራሮችን አባሮ ይህ የፀደቀው በመቀሌ ካድሬዎች ነው፡፡ ይህ ህገ መንግስታዊ አይደለም፡፡ የድርጅቱ ህገ ደንብም ይከለክላል፡፡ ይህ ጠቅላላ ጉባዔ ሳይወስን ነው የተባረሩት፡፡ በዚህ ላይ ልዩነት ነበርን፡፡ሁለተኛው የኢህአዴግ ማዕከላዊ ጉባዔ ሲደረግ አቶ መለስ ስለ አካሄዱ ሲገልፅ አንዳንድ የማይመቹ ቃላት ተናገረ፡፡ እኔም እጄን አውጥቼ ‹‹አነጋገርህ አላማረኝም አሁንስ መንግስቱን መሰልከኝ›› አልኩኝ፡፡  የአይዲዮሎጂ ልዩነትም ነበረን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ደጋግመው ዴሞክራሲ ስለመቀጨጩ ነግረውኛል፡፡ ግን ሁለት ጊዜ ተወዳድረው ፓርላማ ገብተዋል፡፡ ታዲያ ዴሞክራሲ የለም ማለት ይችላል?

ዶክተር ነጋሶ፡- በወቅቱ ስብሰባ ለማካሄድ፣ ሰልፍ ስንጠራ ተከልክለናል፡፡ ሚዲያው ምን ዓይነት ነፃነት አለው? 1997 ዓ.ም ምርጫ በተመለከተ አይተናል፡፡ ብዙ ችግሮች ቢኖሩም ተቃዋሚዎች ውጤታማ ነበሩ፡፡ ሚዲያውም ክፍት ነበር፡፡ በምርጫ ወቅትም ብዙ ጣልቃ ገብነት አልነበረም፡፡ ከዚያ በኋላ የወጡትን አዋጆች አይተናል፡፡ በወቅቱ ጥሩ ነገር ተሰርቶ ነበር፡፡ ለካድሬዎች መመሪያ ተሰጥቶ ነበር፡፡ የምርጫ መመሪያ ለአባሎቹ በትኗል፡፡ ያም ሆኖ ደንቢዶሎ በምወዳደርበት ወቅት ፈተና ነበር፡፡ ካድሬ ሲረብሽ ህዝቡ ነበር ሥርዓት የሚያሲዘው፡፡ የምርጫ ቅስቀሳውም በዚያው ልክ ፈተና ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡- አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  ውስጥ ናት፡፡ መሆን ነበረበት?

ዶክተር ነጋሶ፡- ባለፈው ጊዜ በተለያዩ ምክንያች ችግሮች ተፈጥረው ነበር፡፡ በእኔ እይታ በጊዜ ቢፈቱ ኖሮ ሁሉም ችግሮች አይከሰቱም ነበር፡፡ ሄዶ ሄዶ በእነዚህ ‹‹ውሃ መልስ ውሃ ቅዳ›› በሚባሉ ሁኔታዎች ነገሮች ተባብስው መጥፎ ውድመቶች ተካሂደዋል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ውስጥ በኢሬቻ በዓል ላይ በተፈጠረው ችግር በተቀሰቀሰ ቁጣ በአንድ ሳምንት 130 ፕሮጀክቶች ሲወድሙ ያሳዝናል፡፡ ከቁጥጥር ውጪ ሲሆን አዋጁ ታወጀ፡፡

በዚህን ጊዜ ምን ታደርጋለህ? ከቁጥጥር የወጣውን ለማስቆም ሌላ ዘዴ ነበር? ጥያቄው ቶሎ ብሎ ወደ መደበኛ ሁኔታ መልሶ ህዝቡም መንግስትም ከሚመለከታቸው ጋር ተወያይቶ ችግሮች እንዲፈቱ ማድረግ ነው፡፡ እኔም ብኖርበት ወይ መልቀቅ ካልሆነ ግን ይህን አይነት እርምጃ መውሰድ አለብኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ሌላው ጥልቅ ተሃድሶ ተደርጎ የአመራር ለውጥም እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

 ዶክተር ነጋሶ፡-  የነበረው «መሃይምም ሆኖ በድርጅት የሚያምን» የሚለው አባባል ተለውጦ ምሁራን ሲሳተፉበት በእውቀት ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ማስፈፀም ሁኔታ እንዲፈጠር መንገድ ይከፍታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የድርጅት አባል ያልሆኑ አሉ ይህም ጥሩ ነው፡፡ ግን ይህ ሁሉ መሰረታዊ የፖለቲካ፣ መልካም አስተዳደር፣ የሙስና ጉዳይ፣ ከህገ መንግስቱ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች በትክክል ተግባራዊ እስካልሆኑ ድረስ የሰዎች መለዋወጥ ችግሮችን ያራዝማል እንጂ ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም፡፡

አዲስ ዘመን፡- የአገር ርዕሰ ብሄር ሆነው ስንት ዲፕሎማቶችን እንደሸኙ እና እንደተቀበሉ ያስታውሳሉ?

ዶክተር ነጋሶ፡- ስንት ዲፕሎማቶች እንደተቀበልኩና እና ሽኝት እንዳደርኩላቸው በቁጥር አላስታውስም፡፡ ግን በርካቶች ናቸው፡፡ 

አዲስ ዘመን፡-  ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

ዶክተር ነጋሶ፡- አመሰግናለሁ።

ክፍለዮሐንስ  አንበርብር

 

Published in ፖለቲካ

የዓለም  የመረጃ ስርዓት  ህዝቦችን በአንድ ገበታ እስከማቋደስ ዘምኗል፡፡በሀገራችንም ከዚህ አኳያ በተለይ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢ የሚገኙ  የመጀመሪያው ትውልድ የሚባሉት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምንም ዓይነት  ርቀት ሳይገድባቸው  አንዲት መጽሐፍን  በጋራና  በአንድ ጊዜ እስከ መጠቀም በሚያስችላቸው የኢትዮጵያ ትምህርትና ምርምር ኔትወርክ ወይም  የተጠናከረ የአይሲቲ አገልግሎት  እስከ መተሳሰር   ዘልቀዋል፡፡

ቀዳሚው የቱ እንደሆነ ባይታወቅም ጅማና መቐለ   ዩኒቨርሲቲ  ከበር እስከ  መመገቢያ አዳራሽና ዶርምተሪ  ተማሪን  በቀላሉና  በፍጥነት የሚያስተናግዱበት የዘመነ  መረጃ አያያዝ ስርዓት  ያላቸው መሆኑን በተለያየ ጊዜ በዚሁ ጋዜጣ መዘገባችንም አይዘነጋ፡፡ጅማና  መቐለ   ዩኒቨርሲቲ  የተማሪን  መታወቅያ ካርድ   ኤሌክትሮኒክስ  እስከ ማድረግ ሄደዋል፡፡ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም የተማሪዎች የመረጃ ቋት በመገንባት በሥራ ላይ አውሏል፡፡የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምንጭ ሲሆን የሚታየውን  የግዢ ስርዓት  በአግባቡ ማስተናገድ የሚያስችል ሶፍት ዌርም ሰርቷል፡፡በዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ማተቤ ታፈረን አነጋግረናቸዋል፦

አዲስ ዘመን፦ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ያለው የመረጃ አያያዝና ያመጣው ለውጥ ምን ይመስላል?

 ዶክተር ማተቤ ፦ እንደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አሰራሮችን በተቻለ መጠን በሲስተምና በስርዓት የመምራት፣ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ የመጠቀም ፍላጎት አለ።ለአብነት ያህል ቀደም ሲልም«ስቱደንት ኢንፎርሜሽን  ማኔጅመንት ሲስተም»የተሰኘ የተማሪዎች የመረጃ ቋት ሰርተን በስራ ላይ አውለናል።የመረጃ ቋቱን ለበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ያበረከትነው ሲሆን በአሁኑ ሰዓት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።  የመረጃ ቋቱ  ከተማሪ ምዝገባ ጀምሮ ተመርቆ እስከ ሚወጣ ድረስ የዘለቀ አገልግሎት የሚሰጥ ነው።አጠቃላይ ገብቶ የሚወጣውም  በዚሁ ሲስተም ነው።በመሆኑም ቋቱ አያሌ ሥራዎችን አቅልሎልንና ችግሮችን ፈትቶልናል። የፀደቀ ግሬድ ጠፋብኝ የሚሉ ቅሬታዎችም መፈጠር ትተዋል።ማን እንደሚያስገባ፣ማን እንደሚያፀድቀው፣ መቀየር ሲያስፈልግ ማን እንደሚቀይረው የተቀመጠ ነገር ስለሆነ አሁን እንደ ዱሮው ግሬድ ጠፋብኝ፣ ተጭበረበረብኝ የሚባል ችግር የለም።

አዲስ ዘመን፦ከዚሁ የመረጃ አያያዝ ሳንወጣ በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭ የሆነውን የግዥ ስርዓት መስመር በማስያዝ በኩል ሶፍት ዌር ሰርታችኋል የሚለውንም ቢያብራሩልን?

ዶክተር ማተቤ፦ ከሶፍት ዌር ጋር ተያይዞ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግዢ ስርዓቱን የሚያሳልጥ የግዢ ሶፍት ዌር አዘጋጅቷል። በዚህ ሶፍት ዌር አማካኝነት በተለይ የንብረት ምዝገባን አስመልክቶ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በእያንዳንዱ ስታፍ ምን ንብረት እንደወጣ፣ስቶር ውስጥ ምን ዓይነት ዕቃ እንዳለ በቀላሉ ማወቅ ተችሏል።የግዢ  ስፔስፊክሽንም በአይሲቲ መሰረተ ልማት ሆነ ማንኛውም ጉዳይ በሲስተም ነው የሚያልቀው።ይሄን ማድረግ የሚያስችለውን ሶፍት ዌር ሌሎች ቢሮዎች ሳይቀር እየወሰዱት ነው። በአገር አቀፍ ደረጃም የመሸጥ ፍላጎቱ አለን። በዚህ በኩል ሶፍት ዌሩን መጠቀም እንፈልጋለን ከሚሉ ተቋማት ጋርም  ግንኙነት ጀምረናል። በተጨማሪም ስንት ሰው ነው ያለው፣በምን ያህል የትምህርት ደረጃ፣በምን ያህል ስብጥር የሚሉና ከሰው ሀብት አያያዝ ጋር በተያያዘ ዩኒቨርሲቲያችን  ሁልጊዜ በትምህርት ሚኒስቴር ሲጠየቅ የሚቸገርባቸውና ግልፅ ያልነበሩ የሰው ሀብት ጉዳዮችን  በሶፍት ዌር ለማድረግም  እየሰራን ነው ያለነው። በዚህ በኩል ያለው በአይሲቲ መሰረተ ልማትም  ሶፍት ዌር እየተጠናቀቀ ነው። ሶፍት ዌሩ ሲጠናቀቅና ወደ ሥራ ሲገባ የሰው ሀብት አመራር ጉዳይ  ግልጽ ይሆናል። የሰው ሀብት ብቻ ሳይሆን የተማሪዎች ካፍቴሪያም በካርድ ሲስተም  ሶፍት ዌር የመስራት ፍላጎት አለ።ይሄን ጅምር ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በይፋ እናወጣዋለን። በተጨማሪም የመምህራን የሥራ ግምገማም በሶፍት ዌር እንዲሆንና ተማሪዎች በዚህ እየገቡ እንዲጠቀሙ የማድረግ ፍላጎት አለ።ይሄም እየተጠናቀቀ ነው።በአጠቃላይ  ዘመናዊ የመረጃ አያያዝን አስመልክቶ በተቋማችን በአይሲቲ መሰረተ ልማት ጥሩ ጥሩ ጅማሬዎች አሉ።

አዲስ ዘመን፦ ጅማሬዎች በአይሲቲ መሰረተ ልማቱ በቂናቸውና ምንም ተግዳራቶች የሉባቸውም ማለት ይቻላል?

ዶክተር ማተቤ፦ ጥሩ ጥሩ ጅማሬዎች ቢኖሩም እነዚህ ጅማሬዎች በራሳቸው በቂ ናቸውና ተግዳሮቶች የሉባቸውም  ማለት አይቻልም፡፡ለምሳሌ፦ የኔትወርክ መቆራረጥን ማንሳት ይቻላል።የሰለጠነ ባለሙያ፣ ስታንዳርድ አለመኖርና ሌሎች በርካታ አወዛጋቢ ችግሮች ቢኖሩም  ዞሮ ዞሮ በራሳችን በመሞከር እየሄድንበት ነው ያለው። 

አዲስ ዘመን፦ ዩኒቨርሲቲያችሁ በአይሲቲ መሰረተ ልማት በኩል አርዓያ ወይም ደግሞ ሞዴል ነኝ ብሎ ያስባል?

ዶክተር ማተቤ፦  በአይሲቲ መሰረተ ልማት በኩል አርዓያ ወይም ደግሞ ሞዴል ማነው ለሚለው  ምላሽ ትምህርት ሚኒስቴር የሚመልሰው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ስታንዳርድ በሌለበትና እንደ አዲስ እየመጣንበት ባለው ሁኔታ ይሄ ተቋም  ነው ቀዳሚው ማለት ያስቸግራል። በግዢ፣በንብረት አያያዝ፣በተማሪ ውጤት  አያያዝ የትኛውና ማነው የሚሻለው የሚለውን ለይቶ ለማወቅ ቁጭ ብሎ መገምገም ያስፈል ጋልም።የመቐለ፣ የጅማ ፣የባህር ዳር ነው የሚሻለው ለማለት የሚቻለውም ከገመገምን በኋላ ነው።ሆኖም ለጊዜው እንደእኔ፣እንደኔ ዩኒቨሪሲቲዎች አሁን በየራሳችን እየሄድን ያለንበት ሁኔታ በፊት ያልነበረ ከመሆኑና ባለሙያዎች ከመነቃቃታቸው ጋር  ተያይዞ ጥሩና ወደ  ስታንዳርድ የሚያመጣ ነው።

አዲስ ዘመን፦ እንደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማረጋገጥና ለማስቀጠል ምን ስልት አለ?

ዶክተር ማተቤ፦ እንደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማረጋገጥ የምንጠቀምባቸው በርካታ ስልቶች አሉ።አንዱና ዋናው አደረጃጀት መፍጠር ነው በተማሪም፣ በመምህሩም፣ በአመራሩም፣በአስተዳደርና ድጋፍ ሰጪው ሰራተኛም የተለያየ አደረጃጀት ተፈጥሯል።ይሄ ብቻ ሳይሆን በመጀመሪያ ሰላማዊ መማር ማስተማሩን ስንጀምር ከሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር አሁን ያለንበት ሁኔታ ምንድነው፣ምን ችግሮች አሉ፣ለወደፊቱ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ምን    እናድርግ፣    እንዴት  እንፍታ ቸው? በሚል ቁጭ ብለን ገምግመን ነው ወደ ስራ የገባነውም። ይሄ በብዙ መልኩ ተሳክቶልናል።የተሳካበትን መንገድ መግለፅ ካስፈለገ  በየጊቢው ሚኒ ኮማንድ ፖስት አለ።የእያንዳንዱ ጊቢ ኮማንድ ፖስት በምክትል ፕሬዚዳንቶች ነው የሚመሩት። የተማሪዎችን ሕብረትና የሴኔት መሪዎችን ጨምሮ በየሳምንቱ ነው የምንገመግመው።የመስተንግዶ፣ዶርምተሪ አካባቢ ያሉና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች   በየሳምንቱ በመገምገም ይፈታሉ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ከተማ አስተዳደሩን ጭምር የሚሰበስበው ኮማንድ ፖስት አለ። በአጠቃላይ ችግሮች ሲከሰቱ ወድያው፣ወድያው ነው የምንፈታቸው።ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከችግሮች ባሻገር አብዛኛው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያስኬደው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተፈጠረው የኮማንድ ፖስት አደረጃጀት ነው።ከዚህ በኋላም ቢሆን ከተማሪዎችና ከሰራተኞች ጋር ጥሩ መስተጋብር አለን።አመራሩም በተገቢው መንገድ ተናቦ ነው የሚሰራው።በመሆኑም ቀጣዮቹን ወራቶች ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማሩን ሂደት  በዚህ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ይቀጥላል የሚል ዕምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፦ እንደ ተቋም በዩኒቨርሲቲው ከነበሩና  በኮማንድ ፖስቱ ከፈታችኋቸው ችግሮች ለአብነት ቢጠቅሱልን? 

ዶክተር ማተቤ፦ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ የሆነ ከፍተኛ የመብራት ችግር ነበረብን።ይሄን ችግር ለሁሉም ጊቢዎች ጀነሬተር እንዲገዛና በሁሉም ጊቢዎች አውቶማቲክ እንዲሆን በማድረግ ፈተነዋል።ሌላው የነበረብን ችግር ውሀ ሲሆን በራሳችን ጉድጓድ በመቆፈርና ከከተማው አስተዳደር ጋር በመነጋገር ለዩኒቨርሲቲው በተለየ መንገድ  ሳይቋረጥ  ውሃ እንዲላክ አድርገናል።አንድ ጊዜ መንገድ በመዘጋጋቱና የትራንስፖርት እጦት በመኖሩ ከገጠመን ችግር በመነሳትም ሱቅ ቢዘጋና አቅርቦት ባይኖር ተማሪዎቻችንን ቢያንስ  ለአንድ ወር መመገብ የምንችልበት ክምችት እንዲኖር በማድረግም ከምግብ አቅርቦት ጋር ሊከሰት የሚችልን ችግር ፈትተናልም።ይሄን ለአንድ ወር የሚሆን ክምችት በየአንዳንዱ ጊቢም ያሟላንበት ሁኔታ አለ።

አዲስ ዘመን፦ ይሄ ማለት ከግዥ ስርዓት ጋር በተለይም ከተማሪ ቀለብ ጋር በተያያዘ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የገጠመው ወይም ሊገጥመው የሚችል ተግዳሮት የለም ማለት ነው?

ዶክተር ማተቤ፦ የግዢ  ስርዓቱ ከፍተኛ ማነቆዎች ያሉት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግሩን  በዝምታ ማለፍ ችግር የለም ማለት አይደለም፡፡ግዢ የሚፈፀመው በዕቅድ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ግዢ ከዕቅድ ውጭ ሊፈፀም ይችላል፡፡ለምሳሌ፦ ለተማሪዎች   ቀለብ የሚውል ጤፍ ያቀርቡ የነበሩ በግርግሩ ሰሞን ትራንስፖርት ስለተቋረጠ አናቀርብም ያሉበት ሁኔታ ነበር፡፡በዚህ ጊዜ ደግሞ የግድ እንጀራ ወደ መግዛት ነው የተሄደው፡፡ነገር ግን የእንጀራ ግዢ የሚፈፀመው ደግሞ በግዢ ስርዓት ነው፡፡በመሆኑም  የግዢ  ስርዓቱ  ይሄን የተቋማቱን ተጨባጭ ሁኔታ ማገናዘብ አለበት የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ለአንድ ወር የሚበቃ የቀለብ ግዢ ብንፈጽምም ግዢው የዩኒቨርሲቲዎቹን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ ባለመሆኑ ከመስመር ውጭም የገዛናቸው ነገሮች የሉም አይባልም፡፡

አዲስ ዘመን፦  ሴቶችን ወደ አመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት በማምጣት በኩል በተቋማችሁ  ያለው ምንድነው?

ዶክተር ማተቤ፦ እንደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በዝቅተኛ፣ በመካከለኛና በከፍተኛ ደረጃ  ሴቶችን ወደ አመራር የማምጣት ፍላጎት አለ፡፡ይሄን ፍላጎት መሰረት አድርገን በሁሉም ደረጃ ወደ ውሳኔ ሰጪነትና ወደ አመራርነት ያመጣናቸው ሴቶች አሉ፡፡በተለይ በከፍተኛ ደረጃ የትምህርት ዝግጅታቸው ዶክተሬትና ማስትሬት የሆኑ ሁለት የዩኒቨርሲቲ  ምክትል ፕሬዚዳንቶች ወደ አመራርነት  አምጥተናል፡፡ይሄ የሆነው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው አመራሮች ቁርጠኝነትና በተቋማቱ ሴቶችን ወደ ውሳኔ ሰጪነትና አመራርነት ለማምጣት ቀደም ሲል ትምህርት ሚኒስቴር አስቀምጦት በነበረ አቅጣጫ ነው።ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሴት በመመራትም በአገሪቱ ቀዳሚ ተሞክሮ የነበረው ከፍተኛ ትምህርት ተቋምም ነው።

አዲስ ዘመን፦በዝግጅት ክፍሉ ስም እናመሰግናለን።

ዶክተር ማተቤ፦እኔም በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስም አመሰግናለሁ።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።