Items filtered by date: Tuesday, 14 February 2017
Tuesday, 14 February 2017 18:43

ለሰው ብሎ ሲያማ

 

አሽከርካሪዎች የትራፊክ ህግና ደንብን ሲተላለፉ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ይታወቃል፡፡ ይህም አስተማሪ መሆን እንደሚኖርበት ይጠበቃል፡፡ ይሁንና በሀገራችን ቅጣቱ ሳይፈጸም እየቀረ ወይም ባግባቡ ባለመከናወኑ የተነሳ ወይም ቀጪው ህግ አስከባሪው እየሆነ የቅጣት ነገር እንደነገሩ እየሆነ በመምጣቱ ሳቢያ አሽከርካዎች ከጥፋት ሲማሩ አይስተዋልም፡፡ የተሸከርካሪ አደጋ በየጊዘው እየጨመረ የሚያጠፋው የሰው ሕይወትና የሚያጎድለው አካል የሚያወድመው ሀብት ከፍተኛ እየሆነ ለመምጣቱም አንድ አብይ ምክንያት እየሆነ ነው  ቢባል የተሳሳተ አይሆንም፡፡

በሀገራችን በተሸከርካሪ ከሚደርሱ አደጋዎች መካከል ጠጥተው በሚያሽከረክሩ የሚደርሰው አደጋ በቀላሉ የሚታይ ባለመሆኑ የተነሳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትራፊክ ፖሊስ አሽከርካሪዎች ጠጥተው እያሽከረከሩ መሆን አለመሆናቸውን በትንፋሽ ምርመራ የሚለይ መሳሪያ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል፡፡ አደጋውን ከመከላከል አከኳያ ይህ አንድ እርምጃ ሊሆን ይችላል፡፡ በስፋትና በዘላቂነት ተግባራዊ መደረግ ግን ይኖርበታል፡፡

ለትራፊክ አደጋ መባባስ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል አግረኞችም ይገኙበታል፡፡ በሀገራችን እግረኞች ከመንገድ ማቋረጫ  (ከዜብራ ማቋረጫ)  ውጪ በተከለከለ ቦታ ሲያቋርጡ መመልከት ተለምዷል፡፡ በዚህም የተነሳ አደጋ ሲደርስ፤ የተሸከርካሪ እንቅስቃሴ ሲስተጓጎል እየተስተዋለ  ነው፡፡ አሽከርካሪዎችም እኛ ብቻ ለምን ጥፋተኛ እንደረጋለን ፤ እግረኞችም ጥፋተኞች ናቸው ሲሉ ይደመጣል ፡፡

እግረኞች በተገቢው ስፍራ ካለማቋረጥ በተጨማሪ በተሸከርካሪ መንገድ ውስጥ ገብቶ በመሄድም  በተለይ እንደ አዲስ አበባ  ባሉ የሀገሪቱ ከተሞች ተለምዷል ፡፤ አዲስ አበባ ሰውና ተሸከርካሪ እየተጋፉ የሚሄዱባት ከተማ አየተባለቸም ነው፡፡ ሰው ከተሸከርካሪ በሬ የሚፈራባት እየተባለችም ነው፡፡

ይህን የእግረኞችን የትራፊክ ህግ መተላለፍ ለመከላከል በአዲስ አበባ አንዳንድ አደባባዮች አልፎ አልፎ የሚከናወኑ ተግባሮች አሉ፡፡ ይህን እንደ ጥሩ ጀምር መውሰድ ይቻላል፡፡

ከወደ ናሚቢያ የተሰማው ወሬ ግን ከዚህ አይነቱ ጥረት ጠንከር ያለ ሆኗል፡፡ የናሚቢያ ፖሊስ እግረኞችን ‹‹ ጠጥታችሁ  በጎዳናዎች ላይ እንዳትንቀሳቀሱ›› ሲል አሳስቧል፡፡ የናሚቢያ ፕሬስ ኤጀንሲ ሰሞኑን ይዞት በወጣው ዘገባው እንዳመለከተው፣ በናሚቢያ ርእሰ መዲና ዊንድሆክ ምሽትና በውድቅት ለሊት አልኮል ከልክ በላይ እየወሰዱ ወደ ጎዳናዎች የሚወጡ እግረኞች ጉዳይ ፖሊስን  በእጅጉ አሳስቦታል፡፡ በዚህ የተነሳም ትራፊክ ፖሊስ እነዚህ እግረኞች የመኪና አደጋ ቢደርስባቸው በአሽከርካሪዎች ላይ እንደሚደረገው ሁሉ የአልኮክል ምርመራ እንደሚደረግባቸው እያሳሰበ ይገኛል፡፡

የናሚቢያ ዋና ከተማ ዊንድሆክ ፖሊስ ቃል አቀባይ  ኤድሙንድ ኮሆሰብ እንደገለፁት፤በተለይ በሳምንቱ መጨሻ ቀናት ሌሊት ላይ እግረኞች የትራፊክ አደጋ ከደረሰባቸው  አልኮል አንድ ሁለት ለማለታቸው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በምሽት ወቅት በአውራ ጎዳናዎች ላይ የሚጓዙ እግረኞች በተሸከርካሪዎች ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ገልጸው፡፡ እነዚህ የአደጋው ሰለባዎች አብዛኛውን ጊዜ በአልኮል ጥንብዝ ብለው ከመሸታ ቤቶቹ የሚወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች መንገዱን ይዘው ለመሄድ የሚቸገሩ መሆናቸውም ነው ያብራሩት ፡፡

ቃል አቀባዩ የትራፊክ ፖሊስ እግረኞች በጥንቃቄ መንገድ እንዲያቋርጡ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ መጀምሩን ጠቅሰው ፣ ህጉን በሚተላለፉ እግረኞች ላይ ግን ተገቢውን እርምጃ እንደሚወሰድ አስገንዝበዋል ፡፡

   ይህ እግረኞችን የተመለከተ አዲስ የቅጣት እርምጃ በደቡብ አፍሪካም በተመሳሳይ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ዘገባው አያይዞ ጠቁሟል ፡፡  የደቡብ አፍሪካዋ ዌስተርን ኬፕ  ግዛት አስተዳደር ይህን የተመለከተ አዲስ አረንጓዴ ካርድ የተሰኘ ህግ ማውጣቱን      አመልክቷል፡፡ በግዛቲቱ አልኮል ጠጥተው በጎዳናዎች ላይ የሚጓዙ እግረኞች መንገዶችን ባልተገባ ማቋረጥን የመሳሰሉ ያልተገቡ ባህሪዎችን እንደሚያሳዩ አብራርቶ፤ እግረኞቹ ለመጠጣታቸው በግልጽና ተጨባጭ መረጃ ማሳየት ሳይቻል በመቆየቱ የተነሳ ተጠያቂ ሳይደረጉ መቆየቱን  ዘገባው አያይዞ አስታውሷል ፡፡ አሁን ግን እንደ ናሚቢያ በእግረኞች ላይ ጥብቅ ርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት መደረጉን አስታውቋል፡፡  ለሰው ብሎ ሲያማ ለእኔ ብለህ ስማ ማለትስ ይሄው አይደል!!

 

አስናቀ ፀጋዬ

Published in መዝናኛ

‹‹ሳትደፈር ኖራ ጨረቃም ርቃ

በሰው ተደፈረች ጊዜዋን ጠብቃ ›› የሚለው ዜማ ስንኝ የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃን በመርገጡ በምርምር ሊደርስበት የሚችለውን ልህቀት በተገቢው የተመለከተበት  ይመስለኛል፡፡

ሕይወት ባመዛኙ ችግርና መፍትሄ ተሳስረውና ተደባልቀው አንዳንዴም ተዋህደው ማብቂያና ማለቂያ በሌለው ጉዞ ፍሰቱን ጠብቀውና ተከታትለው አንዳንዴም ለኛ ግልጽ  ባልሆነ  ምትና ፍሰት እየተቆራረጡና እየተበጣጠሱ በሚፈራረቅ ዘመን ውስጥ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ወለድ የሆኑ በርካታ ግኝቶች ለዓለም ተበርክተዋል፡፡ 

ቴክኖሎጂ በየፈርጁ በርካታ ግኝቶችን ማበርከቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የኔ ትኩረት ግን በብዙሃን መገናኛ በተለይም በኤሌክትሮኒከስ ብዙሃን መገናኛ ላይ ነው፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በ1850ዎቹ አካባቢ ማርኮኒ ሬዲዮን ፈልስፎ ለዓለም አበረከተ፡፡ ሬዲዮም በዓለም ሰፍቶ ለ100 ዓመታትም በዘርፉ ያለምንም ተቀናቃኝ ብቸኛ ሆኖ ቆየ፡፡

ከብዙ ምርምርና ውጣ ውረድ በኋላ በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ቴሌቪዥን ለዓለም ተዋወቀ ፡፡ ያኔ ሬዲዮ አበቃለት ተብሎም ነበር፡፡ ሆኖም ሬዲዮና ቴሌቪዥን በየራሳቸው ፈርጅ ቀጥለው ዛሬ ላይም እየተገለገልንባቸው እንገኛለን፡፡ እነዚህም የብዙሃን መገናኛ መሳረያዎች ከቤት በተጨማሪ በየተሸከርካዎቹ ተገጥመው እንዲያገለግሉም እየተደረገ ይገኛል፡፡

ዛሬ ዛሬ በአውቶሞቢሎችና በህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ላይ ከሬዲዮ በተጨማሪ እስክሪኖች ተገጥመው ለገበያ እየቀረቡ ናቸው፡፡ ሸማቹም እንደ ፍላጎቱ ይሸምታል፡፡ እነዚህን የብዙሃን መገናኛ ቁሶችም እንደ አስፈላጊነቱ ይገለገልባቸዋል፡፡ ሊገለገልባቸውም ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ጋዜጣ በታህሳስ 25 ቀን 2009 ዓ.ም እትሙ በመዝናኛ አምዱ

‹‹እስክሪኖቹም እንደ ቀበቶዎቹ›› በሚል ርእስ አንድ አጭር ነገር ግን ቁም ነገር ያለው  መጣጥፍ አስነብቦናል፡፡ በየተሸከርካዎች መቀመጫዎቹ ላይ እንዳሉት የአደጋ መከላከያ ቀበቶዎች በሸገርና በፐብሊክ ሰርቪስ አውቶብሶች ውስጥ የተገጠሙት እነዚህ እስክሪኖች አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ፤ ስለሆነም ወይ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረግ፤ አለያም ይሸጡና ለየድርጅቶቹ ገቢ ይሁን የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰ ተገቢ የሆነ ሀሳብ ተሰንዝሯል ፡፡

በህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ተሸከርካሪዎች ውስጥ የሚገጠሙ ዘመናዊ የመልአክት ማሰራጫ ቁሶች በተገቢው ጥቅም ላይ መዋል ከቻሉ ለበርካታ ሕብረተሰብ  (የትራንስፖርቱ ተገልጋይ)  የሰብእና ግንባታ የሚኖራቸው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በእነዚህ ማሰራጫዎች በመገልገል የሚተላለፉ መልእክቶች ተሳፋሪው በጉዞው እንዳይሰላች ከማድረግ ባለፈ ከሌላው ተሳፋሪ ጋር ሀሳብ የሚለዋወጥበትን አጋጣሚ ይፈጥራሉ፤  ለህይወት ጠቃሚ የሆኑ ሀሳቦችን ሊሰሙበት የሚችልበትን ሁኔታ ይፈጥሩለታል፡፡

በከተማችን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የትራንስፖርት እጥረት ያለ በመሆኑ ዋናው ትኩረት የትራንስፖርት አገልግሎትን ማቅረቡ ላይ ሆነ እንጂ እንደተባለው እስክሪኖቹን የመገልገልና ህብረተሰቡን የማሳወቅ የማስተማርና የማዝናናቱ ጉዳይ ቸል የተባለ ጉዳይ አይደለም ፡፡

ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ያሰማራቸው ተሸከርካሪዎች የአካል ጉዳተኞች መግቢያ፣  አቅመ ደካሞችንም ለማስተናገድ ከፍ  ዝቅ ማለት የሚችል ፣ ሴኩሪቲ ካሜራና ሌሎችም ቴክኖሎጂዎች ተሟልተውለት የተፈበረከ ቢሆንም፣ ድርጅቱ እስክሪኖቹንም አንደ አይኑ ብሌን የሚጠብቃቸውና በተሽከርካሪ ሲገጠሙ ለይስሙላ ሲሉ ሰምታ እንደሚሉት አይነት ቢሂል ሆኖበት አይደለም፤ በአግባቡ ለተገልጋዩ ህብረተሰብ የታቀደና የተጠና መልእክት ሊያስራጭባቸው ግብ በማስቀመጡ እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል ፡፡

እዚህ ላይ ሸገር እስክሪኖቹን ለመገልገል ምን እያደረገ እንደሆነ ከመግለጼ በፊት በጨረፍታ ስለተግባቦት ላንሳ፡፡ ተግባቦት  (ኮሙኒኬሽን) መልእክትን ፣ መልእክት ተቀባይንና መልእክት የሚተላለፍበትን መንገድ በዋናነት ማእከል ያደርጋል፡፡ አንድ አካል በየትኛውም መንገድ መልእክት ሲያስተላልፍ ወይም ሲያሰራጭ ሊያገኘው የሚፈልገው ግብ አለው፡፡ ተግባቦት ሳይጠናና ሳይታቀድ የተከናወነ እንደሆነ ያልተፈለገ ግብ  (አን ኢንቴንድድ ሪዘልት) ሊያመጣ ይችላል፡፡  በተለይም ተደራሲው ይብዛም ይነስም የብዙሃን መገናኛን በመገልገል የሚተላለፍ መልአክት ያልተፈለገ ውጤት እንዳያመጣ ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል ፡፡

ሸገርም እስክሪኖቹ ስላሉ ብቻ ባልተጠናና ባልታቀደ አግባብ ወደ ስርጭት መግባት ያልፈለገው የሚተላለ ፍበት መልእክት (ሙዚቃ፣ ፊልም፣ ፕሮግራሞች፣ ወዘተ) ‹‹ እስክሪኖቹ እንደ ቀበቶዎቹ ›› በተሰኘው ርእስ እንደጻፉት  ጸሀፊ ተሳፋሪው በጉዞ እንዳይሰላች ከማድረግ ይልቅ አስቆጥቶትና አበሳጭቶት የታሰበው ቀርቶ ያልታሰበው ሆኖ ያልተገባ ምርት ላለማጨድ በአውቀት  በመታገዝ የዘርፉን ልዩ ባህሪ በማጤን (የባስ ብዙሃን መገናኛ)  ባስ ሚዲያ  ጽንሰ ሀሳብን ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ተግባር ሁሉ አከናውኗል ፡፡

የባስ ብዙሃን መገናኛም  (ባስ ሚዲያ ) የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ሀገራችን በየትም በሁኔታ ያልተተገበረና ሲተገበርም ጥንቃቄን የሚጠይቅ በመሆኑ ሸገር የሌሎች ሀገሮችን ተሞክሮ በማጥናት የባስ ሚዲያ አተገባበር ሥርዓት እያዘጋጀ ይገኛል፡፡ በዚህም በዘፈቀደ ፊልምና ሙዚቃ ከማሰራጨት የተላቀቀ የራሱ የሆነ የጊዜ ሰሌዳ ያለው ለታላሚ ታዳሚው የሚመጥንና በተለያዩ የፕሮግራም አቀራረቦች (ፎርማቶች) የተቀመረ የጉዞውን የጊዜ ርዝማኔ ግንዛቤ ያካተተ የስርጭት መርሀ ግብር እንዲኖርና እንደተባለውም ተሳፋሪው በጉዞው ሀሳብ እየገበየና እየተማማረ ሳይሰለች የሚጓዝበትን ሁኔታ ለመፍጠር በርካታ ርቀቶችን ተጉዘናል ፡፡

አመኑኝ ሸገር እስክሪኖቹ እንዳይገጠሙ ወይም የተገጠሙትም እንዲነቀሉ አያደርግም ፡፡ ይልቁንም እስክሪኖቹ ከተገዙበት ዋጋ በላይ አገልግሎት እንዲሰጡ ግን እናደርጋቸዋለን ፡፡ እስክሪኖቹን በመገልገል የምናሰራጫቸው መልእክቶች ተሳፋሪውን ከትራንስፖርት ተገልጋይነት ባለፈ የስርጭቶቻችን ታዳሚ ያደርገዋል ፡፡

የሸገር የተሽከርካሪ ስክሪኖች  በከተማዋ እንደ አንድ የመገናኛ አውታር የሚያገለግልበት ጊዜም ሩቅ አይሆንም፡፡ ሸገር  ምንም እንኳን ዋና ተልእኮው ተመራጭ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ለከተማው ሕብረተሰብ ማቅረብ ቢሆንም፣ ከዚህ ተልእኮው መሳ ለመሳ ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶችን በማቅረብ የተገልጋዩን ምቾትና ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነቱንም ላፍታም ቢሆን የሚዘነጋው አይሆንም ፡፡

ሸገር ባለበት የትራንስፖርት ችግር አይኖርም !!

አለባቸው እስከዚያው

Published in መዝናኛ

የጤና ባለሙያዎች ለእናቶች ርህራሄና አክብሮት በማሳየት የአመለካከት ለውጥ ሊያመጡ ይገባል፤

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ፤ በ1980ዎቹ መጀመሪያ በኢትዮጵያ ከወሊድ ጋር በተገናኙ ችግሮች ምክንያት ከ100 ሺ እናቶች 708ቱ ለህልፈት ይዳረጉ ነበር። ይህንን ችግር በመሠረታዊነት ለመፍታት የጤና ተቋማት ማስፋፋት፣ የጤና ባለሙያዎችን አሠልጥኖ ወደ ሥራ የማስገባት፣ በጤና ተቋማት ግብአቶችን የማሟልት ተግባራት ተከናውነዋል።

ይህን ተከትሎም የእናቶችን የሞት ምጣኔ በመቀነስ ረገድ አገሪቱ ይበል የሚያሰኝ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ይሁንና አሁንም በወሊድ እና ከወሊድ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ችግሮች ምክንያት ለህልፈት የሚዳረጉ እናቶች በርካታ ናቸው።

ከኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፤ በአሁኑ ወቅትም  ከ100 ሺ እናቶች መካከል  412  እናቶች በወሊድ ምክንያት ለሞት ይዳረጋሉ። ይህ አሃዝ አሁንም በአገሪቱ ያለው የእናቶች የሞት ምጣኔ አገሪቱ ብዙ የቤት ሥራ እንዳለባት አመላካች ነው።

በሁለተኛው የዕድገትና ሽግግር ዘመን የእናቶችን የሞት ምጣኔ ወደ 199 ለማውረድ ግብ ተጥሎ ርብርብ እየተደረገ ሲሆን፤ ለግቡ ስኬት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት ወሳኝ መሆኑ የማያጠያይቅ ነው። በዚህ ረገድ የጉዳዩ ባለቤት የሆኑት የጤና ባለሙያዎች ድርሻ ከፍተኛ ነው።

በየዓመቱ በወርሃ ጥር የሚከበረው የጤናማ እናትነት ቀን ባለፈው ወር «ርህራሄና አክብሮት የተሞላበት የጤና አገልግሎት ለጤናማ እናትነት!» በሚል መሪ ቃል በአገር አቀፍ ደረጃ ለ11ኛ ጊዜ በአዳማ ሜዲካል ኮሌጅ በተከበረበት ወቅት  የኮሌጁ ፕሮቮስት ዶክተር አለማየሁ ግርማ  እንዳሉት ፤ ሁሉም ህብረተሰብ ለእናቶች መስጠት ያለበትን አክብሮት እና ርህራሄ ሊያሳይ ይገባል፡፡  በተለይም በየጤና ተቋማቱ የቅድመ ወሊድ፣ የወሊድ እና የድህረ ወሊድ አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች ለእናቶች ተገቢውን ክብር እና ርህራሄ ማሳየት ይኖርባቸዋል።

የጤና ባለሙያዎች ለነፍሰ ጡር እናቶች  ክብር እና ርህራሄ የሚያሳዩ ከሆነ እናቶች በጤና ተቋማት ላይ ያላቸው መተማመን ከፍ ይላል ያሉት ዶክተር አለማየሁ፣ ይህም በጤና ተቋማት የእርግዝና ክትትል የሚያደርጉ እና የሚወልዱ እናቶች ቁጥር እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑን ነው  ያስረዱት፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶች እና ሕፃናት ጉዳዮች አማካሪ አቶ አሸናፊ ግርማ እንደሚናገሩት፤ ባለፉት ዓመታት በእናቶች ሞት ቅነሳ ላይ የተሠሩ ሥራዎች አመርቂ ውጤቶችን ቢያስገኙም አሁንም ተግዳሮቶች ይስተዋላሉ፡፡

ከእነዚህ ተግዳሮቶች መካከል በጤና ተቋማት ተገቢውን የህክምና ክትትል የሚያደርጉ  እናቶች ቁጥር ከተያዘው ግብ አንጻር አሁንም ዝቅተኛ መሆኑን አቶ አሸናፊ ይገልጻሉ፡፡ በጤና ተቋማት ውስጥ አንድ ጊዜ የህክምና ክትትል የሚያደርጉ እናቶች ቁጥር የጨመረ መሆኑን ጠቅሰው፣ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ አንድ እናት በእርግዝና ወቅት ቢያንስ አራት ጊዜ ክትትል ማድረግ እንደሚኖርባት ነው ያመለከቱት።     

«የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የሚደረገው ርብርብ የሚፈለገውን ውጤት ሊያስገኝ የሚችለው ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ የእርግዝና ክትትል የሚያደርጉ እናቶች ቁጥር ከፍ ሲል ነው» የሚሉት አቶ አሸናፊ፣ የቅድመ ወሊድ፣ የወሊድ እና የድህረ ወሊድ የእናቶች የህክምና ክትትል ከታሰበው ግብ አንጻር አሁንም ዝቅተኛ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

እንደ አቶ አሸናፊ ማብራሪያ ፤ የነፍሰ ጡር እናቶችን የህክምና ክትትል ከፍ በማድረግ የእናቶችን የሞት ምጣኔ ለመቀነስ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጤና ባለሙያዎች ርህራሄ እና አክብሮት የተሞላበት አገልግሎት በተለይም ለእናቶች  እንዲሰጡ ለማድረግ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው።

የህክምና ባለሙያዎች ለእናቶች ርሁሩ መሆን እናቶች ያለምንም መሸማቀቅ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የቅድመ ወሊድ፣ የወሊድ እና የድህረ ወሊድ አገልግሎቶችን ስለሚያገኙ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ለሚሠረው ሥራ እገዛ ያደርጋል።

የጤና ባለሙያዎች የባህሪ ለውጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው በመጠቆም ነፍሰ ጡር እናት የህክምና ክትትል ካልተደረገላት ለችግር ልትጋለጥ እንደምትችል በመገንዘብ እያንዳንዱ ዜጋ እናቶች ወደ ህክምና ተቋማት እንዲሄዱ በማስገንዘብ፣ ርህራሄ እና አክብሮት በማሳየት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶች እና ሕፃናት ጉዳዮች ባለሙያ አቶ ስንታየሁ አበበ እንደሚናገሩት፤ በጤና  ተቋማት መካከል የእናቶች ቅብብሎሽ መጠናከሩ ፣ በጤና ተቋማት የሚሰጠውን የእናቶችንና  የሕፃናትን ጤና አገልግሎት በነፃ እንዲሰጥ መደረጉ፣ የድንገተኛ ቀዶ ጥገና አገልግሎት በየአካባቢው መስፋፋት፣ ለእናቶች ጤና መሻሻል እና ለእናቶች ሞት ቅነሳ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በጤና ተቋማት ለእናቶች የወሊድ አገልግሎት የሚሆኑ የግብዓት ግዢና ስርጭትን ማጠናከር፡ በጤና ተቋም የድህረ ወሊድ ቆይታን ከ24-48 ስዓት እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ስንታየሁ ገለጻ ፣ከዚህ ጎን ለጎን እናቶች አገልግሎት ያገኙ ዘንድ የማቆያ ስፍራና ግብአቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን በጤና ተቋማት ውስጥ በማሟላት ለእናቶች ሞት ቅነሳ ሠፊ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም በእርግዝና ወቅት አደጋ ሲያጋጥምና በምጥ ጊዜ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ አገልግሎት ለማግኘት ሲኬድ የውሳኔ መዘግየት፤ ከቤት እስከ ጤና ተቋም ለመድረስ መዘግየት፤ ጤና ተቋም ከተደረሰ በኋላ የሚያጋጥሙ መዘግየቶች አሁንም በኢትዮጵያ ለእናቶች ሞት መከሰት ምክንያት እየሆኑ እንደሚገኙ ነው አቶ ስንታየሁ ያብራሩት።

ዶክተር አለማየሁ ግርማ እንደሚናገሩት፤ ባለፉት ጊዜያት የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች ለእናቶች የህክምና አገልግሎት በመስጠት ረገድ በርካታ ውስንነቶች እንደነበር አንስተዋል፡፡ በተለይም ለእናቶች ርህራሄ እና ክብካቤ የተሞላበት አገልግሎት አሰጣጥ ችግር እንደነበር አውስተዋል፡፡

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ከባለሙያዎች ጋር ከስምምነት በመድረስ ለሁሉም እናቶች ጥራት ያለው እና ነጻ የወሊድ ክትትል አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች ሰው አክባሪ እና ተንከባካቢ እንዲሆኑ እና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት የመስጠት ልምድ አጠናክሮ ለማስቀጠል በቀጣይነት እንደሚሰራም ነው ያብራሩት ፡፡

ወይዘሮ ኮከቤ ጌታቸው በአዳማ ከተማ የ04 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸውን  በጤና ተቋም ነው የተገላገሉት ፡፡ በጤና ተቋም የእርግዝና ክትትል በማድረጋቸው እና ለወሊድም ወደ ጤና ተቋም በማምራታቸው ያለምንም እንከን የመጀመሪያ ልጃቸውን ለመገላገል መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

በጤና ተቋማት የወሊድ ክትትል የሚሰጡ ባለሙያዎች ክብካቤ እና ጥራት ያለው አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮ ኮከቤ፣ አሁንም ነፍሰ ጡር መሆናቸወንና በአዳማ ሜዲካል ኮሌጅ የእርግዝና ክትትል እያደረጉ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ሌሎች ነፍሰ ጡሮች ወደ ህክምና ተቋማት ሲሄዱ አልፎ አልፎ የሚያመናጭቁ እና ርህራሄ የሌላቸው ባለሙያዎች እንደ ሚያጋጥማቸው እናቶች ሲያወሩ መስማታቸውን ነው የሚያነሱት፡፡ ‘‘ የጤና ባለሙያዎች ክብካቤ እና ርህራሄ ለእናቶች ከምንም የሚበልጥ ማበረታቻ ነው‘‘ የሚሉት ወይዘሮ ኮከቤ፣ ሁሉም ባለሙያዎች ይህን በመረዳት በተቻላቸው አቅም ለእናቶች የተለየ ክብካቤ ሊያደርጉ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

 

መላኩ ኤሮሴ 

Published in ማህበራዊ

የኢፌዴሪ መንግሥት ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ነድፎ መተግበር  በመቻሉ በየዘርፉ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ ተችሏል። በአገራችን ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ከተመዘገቡት በርካታ ስኬቶች መካከል  የታላቁ የኢትጵያ ህዳሴ ግድብ አንዱ ነው ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። ይህ ግድብ አሁን ላይ ግንባታው ወደ ስድሳ በመቶ አካባቢ ደርሷል።

ግድቡ ለኢትዮጵያ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር ፖለቲካዊ ፋይዳውም የጎላ ነው። ምክንያቱም ይህ ፕሮጀክት የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ቀልብ መግዛት የቻለ  በመሆኑ ሁሉም ዜጋ የእኔ ነው በሚል አገራዊ ስሜት አሻራውን እያሳረፈበት ይገኛል። 

አንዳንድ ምሁራንና የታሪክ ተመራማሪዎች ታላቁን የህዳሴ ግድብ እንደ “አድዋ ጦርነት” ሁሉ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን በአንድ ጥላ ስር ማሰባሰብ የቻለና የህዝቦች አንድነት የታየበት፣ ሲሉ ይገልጹታል። እርግጥ ነው በእኛ ዘመን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የትብብራቸው ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

አገራችን በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ቀድሞ ትታይበት የነበረው መነጽር ዛሬ ላይ ተለውጧል። ባለፉት ሥርዓቶች በተለይ በደርግ ወቅት  በነበረው  በእርስ በርስ ግጭት፣ ድርቅና ረሃብ ሣቢያ የአገራችን ገጽታ ክፉኛ ተጎድቷል። ይሁንና ባለፉት 26 ዓመታት መንግሥትና መላው ህዝቦቿ በቅርበት መሥራት በመቻላቸው ተጨባጭ ለውጦች መታየት ችለዋል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የመንግሥትና የህዝብ የቅርብ ትስስር ውጤት ነው። ምክንያቱም በታዳጊ አገር የውስጥ አቅም ብቻ ባለብዙ ቢሊዮን  ዶላር ፕሮጀክት መገንባት የሚታሰብ አይደለም። ግብጽ የአስዋንን ግድብ ስትገነባ በወቅቱ ለግንባታ የሚያስፈልገው አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ወጪ የተሸፈነው ከቀድሞው ሶቭየት ህብረት መንግሥት ነበር። ዛሬ አገራችን ከአራት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሚጠይቅን ፕሮጀክት በራስ አቅም መገንባት መቻሏ አድናቆት ሊያስቸራት የሚችል ጉዳይ ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግደብ ፕሮጀክት ይፋ ሲደረግ በርካታ አካላት የአገራችን የቅርብ ወዳጆች ጭምር ለፖለቲካ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር  እንዲህ ያለ የባለ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪን እና  የካበተ የግንባታ ልምድን የሚጠይቅ ፕሮጀክትን እንደ ኢትዮጵያ ያለች ደሃና ታዳጊ አገር ልትተገብረው አትችልም ሲሉ እቅዱን አጣጥለውት ነበር። በእርግጥ እነዚህ አካላት እንዲህ ያለ አስተሳሰብ ቢፈጠርባቸው የሚገርም አልነበረም። ምክንያቱም በጦርነት፣ ረሃብና ድርቅ ለዘመናት ትታወቅ የነበረች አገር በሁለት አሥርት ዓመታት ብቻ ባገኘችው ሠላምና መረጋጋት እንዲህ ያለ ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪን የሚጠይቅ ፕሮጀክት  ለመተግበር መነሳቷ  አግራሞት  ቢፈጥርባቸው  አያስደንቅም።

ለዘመናት ኢትዮጵያን ሲያስተዳድሩ የነበሩ መንግሥታት አባይን የመጠቀም ፍላጎት ቢኖራቸውም የደፈረ ግን አልነበረም። የኢፌዴሪ መንግሥት ነባራዊ ሁኔታዎችን በአግባቡ ተንትኖ ትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጅን በመንደፍ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፎ አሁን ላይ ፕሮጀክቱ ወደ ውጤት በመቅረብ ላይ ይገኛል። መንግሥት በአባይ ወንዝ ላይ ለሚገነቡ ፕሮጀክቶች  እርዳታም ይሁን ብድር ማግኘት እንደማይቻል በሚገባ ተገንዝቦ  ሌሎች አማራጮችን በመከተል የአገራችንን የዘመናት ምኞት እውን አድርጎታል።

ታላቁ መሪ የዚህን ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ መጋቢት 24/ 2003 ዓ.ም በጣሉበት ወቅት  “ያሉን ሁለት አማራጮች ናቸው፤ አንድም ይህን ግድብ በራሳችን አቅም መገንባት አሊያም ግድቡን ያለመሥራት፤ ይሁንና የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ግድብ በራሳችን አቅም እንገነባለን እንደሚል ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም” ሲሉ ተናግረዋል።

በዚያው ዓመት የግንቦት ሃያ 20ኛው ዓመት በተከበረበት ወቅት ታላቁ መሪ በመስቀል አደባባይ ለተሰበሰበው  ህዝብ ስለታላቁ የህዳሴ ግድብ “ግንበኞቹም እኛው፣  መሃንዲሶቹም እኛው፣ የፋይናንስ ምንጮቹም እኛው” ሲሉ  ግድቡ  በእኛው ለእኛ የሚገነባ መሆኑን  አስምረውበት  ነበር። ይህ ብስልና ታላቅ  ንግግር  አገር ወዳድ  ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከጫፍ እስከ  ጫፍ ለፕሮጀክቱ ድጋፉን በሚችለው ሁሉ እንዲለግስ እንዲሁም ግድቡ የእኔ ነው የሚል ስሜት በህዝቦች መካከል እንዲፈጠር አድርጓል። ይህ ነው አስተዋይነት፤ ይህ ነው ታላቅነት።

ኢትዮጵያ ይህን ግድብ በራሷ ወጪ ትገንባ እንጂ ጠቀሜታው ድንበር ዘለል ነው። የግብጽ አንዳንድ ሚዲያዎችና ፖለቲከኞች ቅንነት በጎደለው ዓይናቸው ተመልክተውት አቧራ ለማስነሳት ሞከሩ እንጂ ያለምንም ወጪ ጥቅም የሚያስገኝላቸው ፕሮጀክት ላይ ነቀፌታ መሰንዘር አይገባቸውም ነበር።

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ለታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ዓመቱን ሙሉ ተመጣጣኝ የውሃ ፍሰት እንዲኖር ያደርግላቸዋል (የአባይ ውሃ ፍሰት በክረምት ከፍተኛ የሆነ፣ በበጋ ደግሞ አነስተኛ የውሃ ፍሰት ያለው በመሆኑ ለመስኖ ልማት አስቸጋሪ ነው)፤ ከደለልና ከጎርፍ ይታደጋቸዋል፤ በተመጣጣኝ ዋጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፤ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ የግድቧን ህይወት ለመታደግ ስትል በዋናው ወንዝና በገባሮቹ ላይ በምትሰራቸው የተፋሰስ ልማቶች የወንዙን ዘላቂ ህይወት ያረጋግጥላቸዋል። የአባይ ወንዝ ላይ ዘላቂ የተፋሰስ ልማት የማይከናወን ከሆነ ዓለማችን በገጠማት የአየር ንብረት ለውጥ ሣቢያ የወንዙ ህይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ጥርጥር የለውም።

የኢፌዴሪ መንግሥት የአባይን ወንዝ የውሃ አጠቃቀም በተመለከተ በኢንቴቤ የናይል የትብብር ማእቀፍ ሲፈረም ጀምሮ የሚያራምደው ፖሊሲ በአገራት መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያስቀድም፤ የሁሉንም የተፋሰስ አገራት ህዝቦች ከወንዙ  “ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍል” እንዲኖር  የሚል መርህን  መሠረት ያደረገ ነው። ይህ የአገራችን  “ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍል” መርህ በታችኞቹ አገራት ጭምር በተለይ በሱዳን መንግሥትና ህዝብ አድናቆት የተቸረው ነው።

መንግሥት የሚከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅና አገራዊ ህልውናችንን የሚያረጋግጥ እንዲሁም በማንኛውም የሌላ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትን የሚከለክል ነው። በዚህ ፖሊሲም አገራችን በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው እጅግ ውጤታማ መሆን ችላለች። የህዳሴው ግድብ ግንባታም የዚሁ ፖሊሲ ውጤት ነው።

የአገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችንም እንደሚቀንስ የመንግሥት ኃላፊዎች በተለያየ ጊዜ ሲገልጹ ነበር። ይህን ታሳቢ በማድረግ መንግሥት ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎችን  በማከናወን ላይ ይገኛል። ታላቁ መሪ መለስ  ሁሉም የአገራችን ጠላቶች ምንጭ ድህነት ነው፤ በመሆኑም ድህነትን መቀነስ በቻልን ቁጥር ጠላቶቻችንም አብረው ይቀነሳሉ  ሲሉ ይናገሩ ነበር።  በመሆኑም የኢፌዴሪ መንግሥት ልማትን ማፋጠንና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ማጠናከር  የሞት የሽረት  ጉዳይ  አድርጎ  ወስዷቸዋል።

መንግሥት ግብርና መር የሆነውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር  ከሚያደር ጋቸው ጥረቶች መካከል የኃይል አቅርቦቱን ማሳደግ አንዱ ነው። ለኢንዱስትሪ መስፋፋት የኤሌክትሪክ ኃይል ትልቅ ድርሻ አለው። ይህ ታላቅ ፕሮጀክት በሙሉ አቅሙ  ኃይል ማመንጨት ሲጀምር የአገራችንን የኃይል አቅርቦት ችግር ትርጉም ባለው ሁኔታ ይቀርፈዋል። ከዚህም ባሻገር ቀሪውን ለጎረቤት አገራት በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ለአገራችን የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ መንገድ ጭምርም ይሆናል።

አገራችን ከድህነት በፍጥነት ልትወጣ የምትችለው እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው። የጀመርነውን ፕሮጀክት በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ማጠናቀቅ እንዲቻል ህዝቡ እስካሁን  እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ዘንድሮ የታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ  የመሠረት  ድንጋይ የተጣለበትን ስድስተኛ ዓመት ስናከብር በጥልቅ ተሃድሶ የለየናቸውን ድክመቶችን በማረም መልካም አስተዳደርን በማስፈን አገራችንን ወደተሻለ የዕድገት ከፍታ በማውጣት መሆን ይኖርበታል። 

 

ወንድይራድ  ኃብተየስ

Published in ፖለቲካ

                  ወይዘሮ አስቴር አማረ፤                                                                        አቶ አበበ ከፈኔ፤

ኢፌዴሪ የህዝብ ተወካች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች  በተሰጣቸው ሃላፊነት መሰረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችንና በስራቸው የሚገኙ ተጠሪ ተቋማትን ይከታተላሉ ፣ ይቆጣጠራሉ፡፡ ድጋፍ በማድረግም ሃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ ይህም ስራቸው የሚከታተሏቸው ተቋማት እቅድ ስኬታማ እንዲሆን ፣ ክፍተቶቻቸው እንዲሞሉና  የህዝብ ተጠቃሚነትን እንዲያሳድጉ ጉልህ ድርሻ እንደሚያበረክት ይታመናል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አካባቢ ጥበቃ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ወይዘሮ አስቴር አማረ እንደሚያብራሩት፤ ቋሚ ኮሚቴው ተቋማት በፌዴራል ደረጃ በተሰጣቸው ተግባርና ሃላፊነት መሰረት እየሰሩ መሆናቸውን ይቆጣጠራል፤ ይከታተላል፡፡  በተቋቋሙበት ዘርፍ ሊተገብሩት ያዘጋጁትን የአምስት አመት እቅድ መሰረት በማድረግ  ስለተከናወኑ ስራዎች ቋሚ ኮሚቴው የክትትልና ቁጥጥር ስራን በመሰራት ገምግሞ አጸድቋል፡፡ ግምገማን የሚያካሂደውም በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳና ሁለተኛውን እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድን ለማሳካት ተቋማቱ እቅዱን ማከናወን የሚችሉ ስለመሆኑ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡

ክትትልና ቁጥጥሩ በዋናነት ትኩረት በማድረግ ተቋማቱ የህብረተሰብ ተጠቃሚነት ላይ ምን ያህል እንደሰሩ ይመለከታል፡፡ በውጤት ደረጃም ለህብረተሰብ ተጠቃሚነት ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ይገመግማል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ ቋሚ ኮሚቴው የሚከታተለው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አካባቢ ጥበቃ ዘርፍ እንደመሆኑ ሰፊ ስራዎችን ይዟል፡፡ ይህ ዘርፍ የኢኮኖሚ አውታሩን የሚዘውሩ ተቋማት  የተካተቱበት ሲሆን፣እነሱም የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር፣ የማእድን ነዳጅና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴርና  13 ተጠሪ ተቋማት ናቸው፡፡ ከነዚህ መካከል ውሃ ልማት ፈንድ፣ የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የአደጋ ስጋት አመራር ኢንስቲትዩት፣ ብዝሃ ህይወት ይጠቀሳሉ፡፡

ተቋማቱ የዝግጅት፣ የተግባርና የማጠቃለያ ምእራፍን ተከትለው የህዝብ ክንፍና ባለድርሻዎችን በማሳተፍና ፍላጎታቸውን በማካተት ስራው በባለቤትነት እንዲሰራ፣ ወደ ለውጥ እንዲገቡና ተገቢውንም ስራ እንዲሰሩ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ክትትሉ የተጠናከረ በመሆኑ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑና በቅንጅት እንዲሰሩ አስችሏል፡፡

ተቋማቱ ባለፉት ዓመታት ሲተገብሩ የቆዩት እቅድን የጋራ ሳያደርጉ እንደነበር ሰብሳቢዋ አስታውሰው፣ አሁን የቀድሞ አሰራር መቀየሩን ነው የተናገሩት፡፡ አመራሮቹ እየገመገሙ፣ ፈጻሚው የጉዳዩ ባለቤት ሆኖ፣ የሚመለከተው ሁሉ እንዲሳተፍ በማድረግ ክፍተቶችን በመለየት እንዲስተካከሉ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ያብራራሉ፡፡

ትግበራው ትልቅ ውጤትና ለውጥ እያስገኘ ነው ይላሉ ወይዘሮ አስቴር፡፡ ከእቅድ ዝግጅት አንስቶ አስከ ትግበራ ያለው አፈፃፀም ግምገማ ይደረጋል ፤ከባለድርሻዎች የሚገኝ ግብአት በእቅዱ ይካተታል ፡፡

እንደሰብሳቢዋ ገለፃ፤ ዘንድሮ የተሾሙ አዳዲስ ሚኒስትሮችንም በቅርበት በማነጋገር እየተሰራ ነው፡፡  የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ አዲስ ቢሆኑም ለስራው አዲስ አይደሉም፡፡ ዘርፉን የሚያውቁ ባለሙያ ናቸው፡፡ በመሆኑም እንደተሾሙ ክትትል አላደረግንም፡፡

‹‹በአካል ጠርተናቸው ምን ላይ ማተኮር እንዳለባቸው አቅጣጫ ሰጥተናል›› ይላሉ፡፡ በተለይ በግዙፍ ፕሮጀክቶቹ ኤሌክትሪክና የመስኖ ስራ ላይ እንዲያተኩሩ በነገርናቸው መሰረት   ሶስቱንም ሚኒስትር ደኤታዎች ይዘው ስራዎቹ ባሉባቸው ክልሎች በአካል በመገኘት ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ጉብኝቱና የተሰጣቸው አቅጣጫ ቴክኒኩንና የአስተዳደር ስራዎችን ለመደገፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ ስራውም በእውቀት እንዲመራ ያስችላል፡፡ 

የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትሩ ዶክተር ገመዶ ዳሌ ዘርፉን እየመሩት ያለው ከብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ተቀይረው ነው፡፡ የማእድን ነዳጅና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳም በተመሳሳይ መልኩ ከውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትርነት ተቀይረው ነው ዘርፉን እየመሩ የሚገኙት፡፡ እነዚህ ሚኒስትሮችም  ዘርፉቸውን አውቀው እንዲመሩ የማድረግ ተግባር ተከናውኗል፡፡ ችግሮች ያሉ ቢሆንም በአፈፃጸም የተሻለ ውጤት እየታየ ነው ሲሉም ነው ወይዘሮ አስቴር ያመለከቱት፡፡

የምንከታተላቸው ተቋሞች የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ማሻሻያዎችን መሰረት አድርገው በመስራት በኩል ገና ጅምር ላይ መሆናቸው የታየባቸው ከፍተት መሆኑንም ሰብሳቢዋ ይጠቁማሉ፡፡ ቁልፍ ችግሮችን ለይቶ በማቅረብ በኩል ተመሳሳይ ውስንነት ይታይባቸዋል፡፡ ቁልፍ ችግሮቻቸውን ካልለዩ ደግሞ ቁልፍ ተግባራቸውን መፈፀም ስለማይችሉ ሊያስተካክሉ ይገባል ነው ወይዘሮ አስቴር የሚሉት፡፡

የበጀት እጥረትም በውስንነት እንደሚነሳ የሚጠቁሙት ሰብሳቢዋ፣ እጥረቱ ያለ ቢሆንም በተሰጣቸው ልክ ያለመስራት፣ እስከ ክልሎችና ወረዳዎች ድረስ መዋቅር ዘርግቶ ተቀናጅቶና አደረጃጀትን ያለመፍጠር፣ የሰው ሃይል እጥረት፣ የባለሙዎች ፍልሰት የጋራ ችግሮች ሆነው እንደሚታዩባችው ይናገራሉ፡፡ ‹‹የዓለም ሁኔታና ገበያው እየተቀያየረ ነው፣ ነገሮችም ባሉበት አይቀጥሉም፤ ስለዚህ ባላቸው በጀት ለመመራት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር አለባቸው፡፡ አንዳንዶቹ ተቋሞችም ወደ አትራፊነት ሊገቡ ይገባቸዋል›› በማለት ያስገነዝባሉ፡፡ ተቋሞች ስለሚሰሯቸው ስራዎች መረጃ ለህዝቡ የማድረስና የግንዛቤ መፍጠር ስራ ውስንነት እንደሚታይባቸውም  ያስገነዘቡት፡፡

አባይ፣ አዋሽና ስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች መልካም ተሞክሮ ያላቸው መሆናቸውን በመግለጽ፤ ተፋሰሶቹ የ10 ዓመታት ስትራትጂክ እቅድ መስራታቸውን ይናገራሉ፡፡ ሌሎቹ ተፋሰሶችም የዚህን መልካም ተሞክሮ ልምድ ሊቀስሙ እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡ የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በአካል ስራዎችን ተመልክተው ቴክኒካልና አስተዳደራዊ ድጋፍ ሰጥተው ወደ ተግባር የገቡበት ሂደት እንደ መልካም ተሞክሮ የሚጠቀስና ሌሎች ሊማሩበት የሚገባው መሆኑንም ይናገራሉ፡፡

እንደ ሰብሳቢዋ ማብራሪያ ፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይልና የኢትጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትም አደረጃጀታቸውን አጠናክረው  የጀመሩት ስራ እንደመልካም ተሞክሮ ይወሰዳል፡፡ ቀደም ሲል ከውጭ አገር ይገዛ የነበረውን ቆጣሪ አሁን (ከሜትክ) ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን መግዛት ተጀምሯል፡፡ ምርቱ በአገር ውስጥ መሸፈኑ በፍጥነት ለተጠቃሚ እንዲቀርብ ያስችላል፣ የአገር ውስጥ አቅምን ያሳድጋል፣ የውጭ ምንዛሪንም ያድናል፡፡

እነዚህ ተቋማት የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያደርጉት ጥረትም በበጎ ጎኑ የሚወሰድ መሆኑን ወይዘሮ አስቴር ተናግረዋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተወካይ አቶ አበበ ከፈኔ እንደሚሉት፤ ቋሚ ኮሚቴው ምክር ቤቱ በህገ መንግስቱ በተሰጠው መብትና በአባላት ሥነሥርዓት ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀፅ 168 ንኡስ አንቀፅ 1 እና 2 በተሰጠው ሃላፊነት መሰረት ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል፡፡ በዚህም መሰረት በስሩ ያሉትን የትራንስፖርት ሚኒስቴርንና 11 ተጠሪ ተቋማቱን ከእቅድ አዘገጃጀት አንስቶ እስከ ትግበራ ክትትል፣ ቁጥጥርና አስፈላጊ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ከሚከታተላቸው፣ ከሚቆጣጠራቸውና ድጋፍ ከሚያደርግላቸው ተጠሪ ተቋማት መካከልም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን፣ የትራንስፖርት ባለስልጣን፣ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ፣ መድን ፈንድ አስተዳደርና የፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎት ድርጅት  ተጠቃሾቹ ናቸው ፡፡

በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥም በሁሉም ተቋሞች የ2008 ዓ.ም እቅድ አፈፃፀም ታይቷል፡፡ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድን መሰረት በማድረግ በጥናት ላይ በመመስረትና ባለድርሻዎችን በማሳተፍ እንዲያቅዱ ጥረት ተደርጓልም ይላሉ፡፡

ግምገማ ከተደረገባቸው መካከል የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለስልጣኑ በአገሪቱ የመንገድ መሰረተ ልማትን በማፋጠን ቀጣይነት ያለው ዕድገት በማስመዝገብ ጉልህ ድርሻ ማበርከቱን ይናገራሉ፡፡ የመንገድ መሰረተ ልማቱ ለእድገት፣ ለማህበራዊና ኢኮኖያዊ ልማትና ወደ ኢንደስትራላይዜሽን ለሚደረገው ሽግግር ተኪ የሌለው ድርሻ እንደተጫወተም አቶ አበበ ይገልፃሉ፡፡

እንደርሳቸው ገለፃ፤ ከ2009 ዓ.ም እቅድ ከተያዘላቸው 216 ፕሮጀክቶች በስድስት ወራት 26 ከእቅድ በላይ፣132 በእቅድ መሰረት ተከናውነዋል፡፡ 19 ከውጭ አገር ተቋራጮች ስምንቱ ፣ ከ32 የአገር ውስጥ ተቋራጮች አራቱ ክንውናቸው ከእቅድ በላይ ነው፡፡ ከስራዎቹ መካከል የመንገዶች ከባድ ጥገና ከታቀደው በላይ፣ ወቅታዊ የመንገድ ጥገና በእቅዱ መሰረት ተሰርቷል፡፡ መሬት መሸርሸርና የመንገድ ዳር አፈር መንሸራተትን የመከላከል ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

በምስራቅና ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች በቋሚ ኮሚቴው የመስክ ምልከታ ተደርጓል የሚሉት አቶ አበበ ፤በአካባቢዎቹ የሚካሄዱት ፕሮጀክቶች ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድልን በመፍጠር አበረታች ውጤት ማሳየታቸውንም ነው ያመለከቱት፡፡ በቴክኖሎጂ ሽግግርና ከምርምር ጋር የተያያዘ ሙያዊ ድጋፍ ለማግኘት ያስቻለ ተግባር መፈጸሙንም ይገልጻሉ፡፡

እንደ አቶ አበበ ማብራሪያ ፤ ሆኖም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት እንዲፈጸሙ ከታቀዱት 216 ፕሮጀክቶች መካከል 43 ፕሮጀክቶች ዝቅተኛ አፈፃፀም ታይቶባቸዋል፡፡ የውጭና የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች በውላቸው መሰረት ፕሮጀክቶቹን አጠናቅቀው ስራ እንዲጀምሩ የማድረጉ ተግባር አጥጋቢ አይደለም ፡፡

የመንገድ ሽፋንን ተደራሽ በማድረግ ሂደት በሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም የ2009 ዓ.ም ስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀም ችግሮችና መንስኤያቸውን ለመለየት ጥረት የተደረገ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ ችግሩን በመፍታት በኩል የሚደረገው ክትትልና ድጋፍ የተጠናከረ አለመሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ከወሰን ማስከበርና ከካሳ አከፋፈል ጋር ተያያዥነት ያላቸው ችግሮች ከመሰረቱ ባለመፈታታቸው ቅሬታዎችና አቤቱታዎች መኖራቸውንም ነው ያመለከቱት፡፡

ካሳ ተከፍሏቸው ንብረት የማያነሱ በተለይም አገልግሎት ሰጪ የሆኑ እንደ ኤሌክትሪክና ውሃ አገልግሎት ያሉ ተቋማት ፕሮጀክቶቹ እንዲጓተቱ በማድረግ ለስራው እንቅፋት እንደፈጠሩ ይናገራሉ፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር መኖሩን በመስክ ምልከታ መረዳት መቻሉን ጠቅሰው ፤ ይህም በየወቅቱ እየተፈተሸ እንዲስተካከል ማሳሰቢያ መሰጠቱንም ይገልጻሉ፡፡

የበጀት እጥረትን ተቋማቱ በተግዳሮትነት እንደሚያነሱም ነው አቶ አበበ የሚገልጹት፡፡ ርክክብ የተደረገባቸው የመንገድ መሰረተ ልማቶች የግንባታ ጥራት ችግር በመኖሩ ክፍተቱ እንዲስተካከል መደረጉንም ተናግረዋል ፡፡

እንደ አቶ አበበ ማብራሪያ፤ የትራንስፖርት ባለስልጣንን የሰው ሀይል የአቅም ውስንነት ለመፍታት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ስምምነት በመፍጠር ፈጻሚዎች እንዲማሩ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባቱ እንዲሁም የፈጻሚዎችንና የመካከለኛ አመራር አካላትን የክህሎት ክፍተትን በአጫጭር ስልጠናዎች ለመሙላት የተከናወኑት ተግባራት በጠንካራ ጎን ተወስደዋል፡፡

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከባለድርሻዎች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት በኩል አሁን ካለው ውጤት ጋር ሲነጻጸር አመርቂ እንዳልሆነም አቶ አበበ ይገልጻሉ፡፡ በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ እየደረሰ ያለው አደጋ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ መፍትሄ እንዲያገኝ መስራት እንደሚያስፈልገም ጠቅሰው፣ ለትራፊክ አደጋ አጋላጭ የሆኑትን ምክንያቶች በመለየት በክፍተቶቹ፣  በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ የሚስተዋሉ የኪራይ ሰብሰቢነት አመለካከቶች ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት ፡፡

ህገ ወጥ  ስምሪትና የሌሊት ጉዞ እንዲገታና መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ ለባለስልጣኑ ማሳሰቢያ እንደተሰጠውም ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ አበበ ማብራሪያ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚታየው የትራንስፖርት እጥረት መፍትሄ ለመስጠት የተወሰዱ ተግባራት ቢኖሩም አሁንም የአቅርቦት ችግር ይታያል፡፡ ለዚሀ ሕብረተሰቡን ከተለያዩ ጉዳዩቹ እያስተጓጎለው ለሚገኝ ችግር መፍትሄ በመስጠት ላይ መግባባት ላይ ተደርሷል ፡፡     

 

ዘላለም ግዛው       

Published in ፖለቲካ

ጥናታዊ ጽሁፎቹ ንግድና ኢንቨስትመንቱ በተሻለ ሁኔታና በተሳለጠ መልኩ እንዲሄድ ይረዳሉ፤

በአገሪቱ ለማማከር አገልግሎት ዘርፍ ይሰጥ የነበረው ግምት አናሳ ሆኖ መቆየቱን የአዲስ አበባ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ሰሞኑን  ይፋ ያደረጋቸው ጥናቶች ያመለክታሉ፣፡

ምክር ቤቱ በሦስት የአማካሪ ድርጅቶች ያካሄዳቸው እነዚህ  ጥናታዊ ጽሑፎች በዘርፉ ዕድሎችና ተግዳሮቶች ዙሪያ፣ የአማካሪ አገልግሎት ከመንግሥት ግዢ  አንጻር እንዲሁም በአገልግሎት ሴክተር ልማት ዙሪያ ያለውን አስተዋፅኦ በስፋት ዳስሰዋል፡፡

 በጥናቶቹ እንደተመለከተው ፤ በማማከር አገልግሎት ከእውቀት ይልቅ ለተግባር ቅድሚያ መስጠት፣ውስን በሆኑ የቢዝነስ ጉዳዮች ላይ ብቻ ማተኮርና ተቋማት ለመማከር አገልግሎት ያላቸው ፍላጎት ዝቅተኛ መሆን የዘርፉ ተግዳሮቶች ሆነው ቆይተዋል።

   አገልግሎት ፈላጊው ከአማካሪዎች ጋር ያለው ግንኙነት የጠበቀ ባለመሆኑ ፍላጎትን የመለየት ችግር፣አማካሪነትን እንደ ትርፍ ጊዜ ሥራ መመልከት ፍትሐዊና ግልጽ የሆነ ፉክክር አለመኖር፣ሙስናና የተጓተተ አሠራር እንዲሁም የግብር ጉዳይ በጥናቶቹ በችግር ከተቀመጡ ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል፡፡

ጥናቱ እንደ መልካም አጋጣሚ ካመላከታቸው መካከል በአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችም ሆነ በቢዝነስ ተቋማት አካባቢ አገልግሎቱን የሚፈልጉ ችግሮች  መኖራቸው፣ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና አማካሪዎች መስፋፋት፣ የማማከር አገልግሎት ፍላጎት መጨመር፣ የግልና የመንግሥት ኢንቨስትመንት ሥራዎች  መስፋፋት ይገኙበታል።

  አቶ ብርሃኑ ራቦ ሞሽን የማማከርና የማሠልጠን ኃለፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (ኮንሰልታንሲና ትሬኒንግ) ተወካይ እንደሚሉት፣ ማማከር  የዕድሜ ጉዳይ ወይም የትምህርት ደረጃ የሚወስን ብቻ ሳይሆን ትልቅ ጥበብን የሚጠይቅ ነው፡፡ ማማከር ለገንዘብ ተብሎ የሚሠራ ሥራ ሳይሆን ማህበረስብ ላይ ለውጥ ማምጣትን እንደ ክፍያ የሚያሰብ ነው፡፡

 በአሁኑ ወቅት የማማከር አገልግሎት  እንደ መልካም አጋጣሚ የሚታየው ሁሉም ሰው ለማወቅና መለወጥ መፈለጉ ላይ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ጠቅሰው፣ የሃገሪቱ ኢኮኖሚም ማደጉና መነቃቃት ማሳየቱ  በራሱ እንደትልቅ አጋጣሚ የሚታይ መሆኑን ያመለከቱት፤ በየትኛውም ዘርፍ ያሉ የቢዝነስ ሰዎች በጭፍን መጓዝ ትተው ወደ አማካሪዎች እየቀረቡ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ብርሃኑ፤ ይህም ለዘርፉ ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱን ነው ያስታወቁት፡፡

 አቶ ብርሃኑ እንዲያም ሆኖ ከዘርፉ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ፈተናዎች ብዙ መሆናቸውን ይገልጻሉ፤ ከዚህ መካከልም አገልግሎቱን ገንዘብ ለማግኛ ብቻ  መጠቀም ደግሞ ተጠቃሽ ችግር መሆኑን ነው የሚያስረዱት፡፡

 የማማከር አገልግሎት የጭንቅላት ሥራ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ  ሥራዎች በሚከናወኑበት ወቅት በፍቅር መሆን እንዳለበትና ፈተናዎች የሚያስቆሙት  መሆን እንደሌለበት አቶ ብርሃኑ ያስረዳሉ፡፡

 የጎልዴ ማኔጅመንት የሥራ አመራር ማማከር አገልግሎት ባለቤትና የአማካሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት እንዲሁም በውይይቱ ላይ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት ዶክተር ዓይናለም አባይነህ እንደሚሉትም ፣በማማከር ዘርፉ እንደመልካም አጋጣሚ ከሚቆጠሩት መካከል በተለያዩ መስሪያ ቤቶች አገለግሎቱን የሚፈልጉ ችግሮች  መኖራቸውና  እነሱን ለመፍታት የሚችሉ አማካሪዎች መፈለጋቸው ይገኙበታል፡፡

 በንግድና ኢንቨስትመንት ዙሪያ የተለያዩ ችግሮች እንደሚስተዋሉ የሚጠቅሱት ዶክተር ዓይናለም፣ዘርፉ ችግሮቹ እንዴት እንደሚፈቱ የሚያሳይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይህ ንግድና ኢንቨስትመንቱ በተሻለ ሁኔታና በተሳለጠ መልኩ እንዲሄድ የሚረዳ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ የማማከር ዘርፉ በንግድና ኢንቨስትመንቱ ላይ  ተግዳሮት ሊሆን የሚችለው  የአመለካከት ችግር ሲፈጠር  መሆኑንም ነው ያመለከቱት፡፡ የዚህ ማሳያው የማማከር አገልግሎቶች መኖራቸውን አለማወቅ፣ አውቆም አለመጠቀም መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡

 የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ዋና ፀሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ እንደሚሉትም፤ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የአገልግሎት ሴክተሩ እያደገ መጥቷል፤ የአገልግሎት ዘርፉ አንዱ አካል ደግሞ አማካሪው ነው፡፡  ስለሆነም አማካሪው አሁን ያለበትን ደረጃ መገምገምና ማየት እንዲሁም የሚሰጠውን ጠቀሜታ ሁሉ  ማጠናከር አስፈላጊ ነው፡፡

የማማከር አገልግሎት ጠቃሚ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ጌታቸው  በተለይ በእውቀት ላይ የተመሠረተ አገልግሎት ለመስጠት ወሳኝ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ የዚህ ሴክተር ማደግና መጠንከር ለኢኮኖሚ  እጅግ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለውም ያክላሉ፡፡ 

የአማካሪዎቹ አቅም ማነስ፣  ከፍቃድ አሰጣጥና  ከአደረጃጀት ጋር ያለ የተወሳሰበ አሠራር፣ የፍቃድና የደረጃ ወጥነት አለመኖሩ፣ እና ሌሎችም የዘርፉ ችግሮች እንደሆኑ ኃላፊው ያብራራሉ፡፡

 ችግሮቹን ለመፍታትም ምክር ቤቱ ሁሉን አቀፍ ጥናት የማካሄድ ጥናቱም አማካሪዎች ለዘርፉ የሚሰጡትን አስተዋፅኦ እንዲለይ የማድረግ ፣ሥራና አቅም ግንባታ ላይ ያላቸውን ሚና የመለየት እንዲሁም አቅማቸውንና ክፍተቶቻቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሥራት ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡

 

አስናቀ ጸጋዬ

Published in ኢኮኖሚ

በአማራ ክልል በቡሬ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የመሰረት ድንጋይ ሲያስቀምጡ፤

 

በምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ መንግስት በእቅድ ከያዛቸው መካከል በቀደምትነት ተጠቃሽ ተግባር ነው፡፡ የውጭ ግብይት ድርሻን ለማሳደግ ወደ ውጭ የሚላኩ የምርት ዓይነቶችን በብዛትና በጥራት መጨመር አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል፡፡ እሴት ጨምሮ ለገበያ የማቅረብ ጉዳይ ከእቅድ የዘለለ ተግባራዊ እንቅስቃሴው እየታየበት አይደለም፡፡

በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ የተገኘው ውጤት እንደሚያሳየው የማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ዘርፍ በዓመት በአማካይ በ17 በመቶ አድጓል፡፡ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ፣ በምግብና መጠጥ፣ በፋርማሲዩቲካል፣ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ፣ ኬሚካል የተሻለ ትግበራ አሳይተዋል፡፡ ሆኖም ለኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን መነሻ የሚሆነው የመካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ልማት ጠንካራ መሠረት መፍጠር አልተቻለም፡፡ በመሆኑም ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ለአጠቃላይ ኢኮኖሚው ያለው ድርሻ ከ5 በመቶ በታች ሆኖ ቆይቷል፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ኤክስፖርት ድርሻ  ካለፉት ዓመታት የተሻለ ቢሆንም በታቀደው ደረጃ የሚለካ አፈፃፀም አልታየበትም፡፡ ሆኖም ገቢ ምርቶች በሚተኩ ኢንዱስትሪዎች ዙሪያ በተለይም በሲሚንቶ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ በብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ የተፈጠረው የፋብሪኬሽንና ኢንጂነሪንግ አቅም መልካም ነው፡፡ በስኳር ዘርፉም ሰፊ የልማት ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ አጠቃላይ ገቢ ምርቶችን በመተካት በኩልም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሰፊ ስራ መስራት እንደሚገባም ተቀምጧል፡፡ 

በእቅድ ዘመኑ የኢንዱስትሪ ልማትና ትራንስፎርሜሽን የሞት ሽረት ጉዳይ በመሆኑ  በዘርፉ የተቀመጡትን ስትራቴጂዎች አሟልቶ መተግበር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሲሆን በመካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ልማት ውጤት ለማስመዝገብ ከምን ጊዜውም የላቀ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠይቅ  ተተንትኗል፡፡

የአገር ውስጥንም ሆነ የውጭ ባለሀብቶችን ፈጥኖ ለማስተናገድና ወደ ምርት እንዲገቡ ለማድረግ፣ ማምረት ከጀመሩ በኋላም ምርታማና ተወዳዳሪነታቸውን ያስተጓጎሉባቸው እንደ የማምረቻ ቦታ እጥረት፣ የመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ የንግድና ጉምሩክ መጓተት እንዲሁም ተያያዥ ችግሮችን ለመቅረፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ማስፋፋት ይገባል የሚል አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

እቅዱ እንዳስቀመጠው፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መሠረት በማድረግ ቀልጣፋና ውጤታማ የመንግስት አገልግሎቶችና ድጋፍ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ የተቀመጡት ማበረታቻዎችም ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው አግባብ በፍጥነት መሰጠት ይኖርባቸዋል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ያሉባቸው ተጨማሪ ችግሮችን ለማቃለል በተደራጁት ኢንስቲትዩቶች አማካይነት ውጤታማ የማኔጅመንት፣ የቴክኖሎጂና የአሠራር ማሻሻያ ድጋፎች በተሻለ ሁኔታ እንዲያገኙ መደረግ አለበት፡፡ የብድር አቅርቦትንም በማሻሻል የኢንዱስትሪ ልማቱን ማፋጠን ይጠበቃል፡፡

ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር  ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር ስኬታማነት የግል ባለሀብቶች ተሳትፎ መጠናከር አለበት፡፡ ሆኖም ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ዘርፉ ለመሰማራት የተለያዩ ውጣ ውረዶች እንደሚገጥማቸው በተደጋጋሚ ሲገለጽ  ይደመጣል፡፡ መንግስት ለዘርፉ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እድገት ውጣ ውረድን ተቋቁሞ ለመስራት ጥረት ማድረግና የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት የሚጠበቅባቸው ቢሆንም ለጉዳዩ ትኩረት ማድረግ ግን አስፈላጊ መሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ነው፡፡

በእርግጥ መንግስት በዘርፉ ለሚሳተፉ ባለሀብቶች የመሬት አቅርቦት፣ አስፈላጊ ጥሬ እቃዎችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባትና ሌሎች የማበረታቻ እድሎች በመስጠት ተጠቃሚ እያደረገ  በዘርፉም በስፋት እንዲሰማሩ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡

በተለይም በክልሎች አስፈላጊ የምርት ግብአቶችን ከማቅረብ ጀምሮ  የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓሪኮችን ማልማት ጠቃሚ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡ በዚህ መነሻነት ፓርኮቹን በአማራ ክልል በቡሬ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡ በሁመራና በራያ አካባቢዎች ለመገንባት  የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል። ይህ ጉዳይም ሰሞኑን በመቀሌ ከተማ በተዘጋጀና የተለያዩ ክልሎች በተሳተፉበት አንደኛው ዙር አገር አቀፍ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ፎረም ላይ ተጠቁሟል፡፡

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአግሮ ፐሮሰሲንግና ፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መብርሃቱ መለሰ በቅርቡ ከጋዜጣው ሪፖርተር ጋር ባደረገቱት ቃለ ምልልስ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያን በ2017 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ እቅድ ተይዞ ለስኬታማነቱ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ በሂደቱም የኢንዱስትሪ ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይጠበቃል፡፡ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ተብለው የሚወሰዱት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፎችም በከፍተኛ ደረጃ ያድጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። 

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አገሪቱን ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ለማድረግ ግብርናን ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ታቅዷል፤ ያሉት  ሚኒስትር ደኤታው፤ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ደግሞ  የመጠጥ ኢንዱስትሪዎችን የሚያጠቃልለው አግሮ ፐሮሰሲንግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ይገኛል፡፡ በዘርፉ ላይም የሀገሪቱን መፃኢ ዕጣ ፈንታ የሚወስነው የምግብ ዘርፍ ተካቷል። 

ዘርፉን አሁን ካለበት ከፍተኛ ጥቅም ሊያስገኝ ወደሚችል ደረጃ ለማሻገር የአግሮ ፐሮሰሲንግ ፓርኮችን ማስፋፋት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ለዚህ ስራም የውጭ ምንዛሬ የሚያስፈልግ በመሆኑ  በተለይ አሁን የተጀመሩት የአግሮ ፐሮሰሲንግ ፓርኮች ግንባታ ከግብርናው ጋር ማስተሳሰር የግድ ይሆናል፡፡ ባለሀብቶች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግም በትኩረት ሊተገበር የሚገባው ነው፡፡ እነዚህን ተግባራት ማከናወን ከተቻለ ወደ ውጭ ምርቶችን በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ይቻላል፣ የስራ እድልም በብዛት ይፈጠራል ሲሉ ነው ዶክተር መብርሃቱ የሚናገሩት።

እንደ ሚኒስትር ደኤታው ገለፃ፤ ለሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ስኬት ፓርኮችን ማልማትና አቅምና ብቃት ያላቸው ባለሀብቶችን መሳብ ያስፈልጋል። ምርቶች ወደ ውጭ ሲላኩና ከውጭ ሲገቡ የሀገር ውስጥ ገቢን በራስ መዳፍ ውስጥ መያዝ፣ የውጭ ውድድርንም መቆጣጠር ያስችላል።

በተለይ ኢትዮጵያ እንደ የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ አገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ)ና የምእራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) የጋራ ገበያ ድርጅቶች አባል ስትሆን የተለያዩ ምርቶችን በቀላሉ ወደ ውጭ ገበያ መላክ ትችላለች። ሆኖም ኢንዱስትሪው ገና ታዳጊ በመሆኑ የገበያው ውድድር የሚወሰነው እንደ ተፈጠረው አቅም ይሆናል። በመሆኑም  የውጭና  የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመቀናጀት ገበያውን እንዲያስቀጥሉ ማድረግ ይገባል ይላሉ።

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የተያዙ የአቅም ግንባታና ምርታማነትን የማሻሻል  ስራዎች አሉ። ለስኬቱ ስትራቴጂክ የሆኑ ዘርፎችም ተመርጠው ጥናት ተደርጎባቸዋል። የእነዚህን ዘርፎች እምቅ አቅም እንዴት መጠቀምና ምን ተግዳሮት እንዳለው ለመረዳት የውጭ ተሞክሮን በመቀመር መሰራት እንዳለበት ታምኖበታል፡፡ አንድ አይነት ምርት ብቻ ሳይሆን ስብጥር ያላቸው ምርቶችን ማምረትም በዕቅዱ ለመተግበር ከተያዘው መካከል ይገኝበታል፡፡

የምግብ የመጠጥና የፋርማሲዮቲካል ዘርፉን የሚቆጣጠር ተቋም ተደራጅቶ ስራ ጀምሯል። በግብርና ዘርፉ ያለው መዋቅራዊ ችግር፣ የፕሮሰስ አቅምና የገበያ ሰንሰለቱ ችግር እስከሚፈታ ድረስ ግብአትን የሚያረጋጋ ተቋም ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ያስፈልጋል ተብሎ በመታመኑ አዲስ ተቋም ተመስርቷል። የአነስተኛና መካከለኛው ማኑፋክቸሪንግ ልማትን የሚመራ ድርጅትም እንደገና በአዲስ መልክ ተቋቁሟል፡፡ በአጠቃላይ እነዚህን ጨምሮ ስምንት የሚጠጉ ተቋማት ተቋቁመው እየሰሩ ናቸው ሲሉም  ዶከተር መብራህቱ ይናገራሉ።

እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ተቋማቱ የቴክኖሎጂ፣ የምርምርና የሰው ሃይል በማሰልጠን እንዲደግፉ የተቋቋሙ ቢሆንም አቅማቸው በሚፈለገው ደረጃ አልተደራጀም።  መሰረተ ልማት ተሟልቶ በቂ በጀት ተይዞ የተጠናከረ ስራ መሰራት አለበት።

የማምረት አቅምን ለመፍጠር ባለሀብትን መሳብ አስፈላጊ መሆኑ ተወስዷል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥሬ ዕቃው ባለበት አካባቢ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማቋቋምና አስፈላጊ መሰረተ ልማትን ማሟላት እንደሚገባ ታምኖበት ለትግበራው ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ በመጠቆም፤ ግብርናው የቅባት እህሎችን በዘመናዊ መንገድና በስፋት አምርቶ ለኢንዱስትሪው እንዲያቀርብ ከዚያም እሴት ጨምሮ በማምረት ደረጃውን ጠብቆ ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ ትኩረት መሰጠቱንም ይገልፃሉ፡፡

 

ዘላለም ግዛው          

Published in ኢኮኖሚ

 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ ተልኦኮ  (ሚኑሲካ) ኤፍ ፒ አር ሲ በተሰኘው ታጣቂ ቡድን ላይ በከፈተው የአየር ድብደባ በርካታ የቡድኑን አባላት መግደሉን አስታወቀ።

ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2012 ጀምሮ በአማጽያንና በመንግስት ሃይል መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ላለፉት አራት ዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ቆይታለች። ኤፍ ፒ አር ሲ በአገሪቱ ካሉት ታጣቂ ቡድኖች አንዱን ትልቁ እንደሆነም የሮይተርስ ዘገባ ያመላክታል። ከቡድኑ አባላት አብዛኞቹ የቀድሞውን የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ቦዚዝ ከስልጣን እንዲባረሩ ያደረገው ‘‘ሴሌካ‘‘ የተሰኘ ቡድን አባላት ናቸው።

በአገሪቱ በተቀሰቀሰው ጦርነት በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ውድ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩት ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ለዓመታት የቆየውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም እስካሁን ማስቆም አልተቻለም። በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የተሰማራው  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ሃይል እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 ወደ ሀገሪቱ አስገብቷል።

ሮይተርስ እንዳስነበበው በትናንትናው ዕለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሄሊኮፕተር ባካሄደው የአየር ድብደባ ባምባሪ ወደ ተባለች ከተማ ሊዘልቁ በሞከሩ ኤፍ ፒ አር ሲ ታጣቂዎች አባላት ላይ ቦንብ ጥቃት አድርሷል፡፡ በድብደባውም የታጣቂ ቡድኑ ከፍተኛ አመራር እና ሌሎች ሶሰት ታጣቂዎች መገደላቸውን የታጣቂ ቡድኑ ከፍተኛ አመራር አስታውቋል።

በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የመንግስታቱ ድርጅት ሰላም አስከባሪ (ሚኑስካ) ቃል አቃባይ ቪላድሚር ሞንቴሪዮ እንደተናገሩት፤ የአየር ድብደባው የተካሄደው ተልዕኮው ለታጣቂ ቡድኑ ያስቀመጠውን ቀይ መስመር በማለፍ ወደ ከተማዋ ሰሜናዊ ክፍል ለመንቀሳቀስ በመሞከሩ ነው።

ከአገሪቱ መዲና ባንጉዌ በ250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ባምባሪ ጦርነት እንዳይከሰት ተልዕኮው ለረጅም ጊዜ ሲከላከል የቆየ ቢሆንም በትናንትናው እለት የተቀመጠውን ቀይ መስመር ማለፋቸው እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማስገደዱን ነው ቃል አቃባዩ የተናገሩት።

ባለፈው ዓመት በአገሪቱ የተደረገው ምርጫ በአገሪቱ አንጻራዊ መረጋጋት እንዲመጣ አድርጎ ነበር። ምርጫውን ተከትሎ ታጣቂዎቹን ወደ ድርድር ለማምጣትና ትጥቅ ለማስፈታት የተለያዩ ሙከራዎች የተደረጉ ቢሆንም በአገሪቱ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ በሚለው የእርስ በእርስ ግጭት ምክንያት ሊሳካ አልቻለም።

የታጣቂ ቡድኑ ምክትል አዛዥ አዞር ካንቴ እንደገለጸው ከሆነ በመንግስታቱ ድርጅት ሰላም አስከባሪ በተፈጸመው የአየር ድብደባ የቡድኑ ከፍተኛ አዛዥ ጆሴፍ ዞንዱኮና ሶስት ዜጎች መገደላቸውን አረጋግጧል። በአገሪቱ በሚገኙ በሙስሊሞችና በክርስቲያኖቸ መካከል ለወራት ከቆየው ምህረት የለሽ መጨፋጨፍ ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት  ሆኖ መቆየቱን ነው ዘገባው ያመላከተው።

ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ ቡድኑ ከመንግስት ታጣቂዎቸ ጋር ከሚያደርገው ጦርነት በተጨማሪ በባምባሪ አካባቢ ከከተመው ዩ ፒ ሲ ከተሰኘው ቡድን ጋር በመዋጋት ላይ የነበረ ሲሆን ውጊያውም በርካታ ሰዎችን ለህልፈት ዳርጓል፤  20 ሺ የሚሆኑ ዜጎችን ደግሞ ከአካባቢያቸው አፈናቅሏል።

በተባበሩት መንግስታተ ድርጅት የዘር ማጥፋት ወንጀል ከፍተኛ አመራር እንደተናገሩት ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ  ኤፍ ፒ አር ሲ በብራይ ከተማ በሚኖሩ የፉላኒ የዘር ግንድ ያላቸው ዜጎች ቤት ለቤት በመፈለግ የግድያ፣ የዝርፊያና የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን መፈጸሙን መግለጻቸውን ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል።

የፕሬዚዳንት ፍራንሷ መንግስት እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን ቀመር በ2007ና በ2010 በአማጽያንና በመንግስት መካከል ለተደረሰው የሰላም ስምምነቶች ተገዥ ያለመሆን በአገሪቱ ጦርነት እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆኑን ሮይተርስ በዘገባው ጠቅሷል።

 

መላኩ ኤሮሴ

Published in ዓለም አቀፍ

230 ሜትር ከፍታ ያለው የኦርቪል ግድብ በ50 ዓመት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ይህ ዓይነት አደጋ ያጋጠመው፤

በአሜሪካ ሰሜን ካሊፎርኒያ የሚገኘውና 230 ሜትር ከፍታ ያለው የኦርቪል ግድብ ያለመጠን በመሙላቱና ማስተንፈሻው ላይ ደረሰ በተባለው እክል ከ180 ሺ በላይ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡

ግድቡ ከሰሞኑ በጣለው ክፍተኛ ዝናብ ምክንያት ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ታሪኩ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከአፍ እስከ ገደፉ ያለመጠን መሙላቱና በዚህም ምክንያት ውሃም አልፎ በመፍሰሱም በአካባቢው ክፉኛ ጉዳት ማድረሱም  ተጠቁማል።

የውሃውን ክፍታ ለመቀነስ የማስተንፈስ ተግባር ቢከናወንም፤ ዋናው የግድቡ ማስትንፈሻ ጉዳት ስለደረሰበት ግድቡ ግንባታ ከተጠናቀቀ ከ1968 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአደጋ ጊዜ ማስተንፈሻውን ለመከፈት የግድ ሆኖ መገኘቱም ታውቋል።

የካሊፎርኒያ ከተማ የውሃ ሀብት ቃል አቀባይ ኤሪክ ሲ፤ የውሃውን ክፍታ ለመቀነስ ግድቡን የማስተንፈሱ ተግባር እንደሚቀጥል ተናግረዋል። የካሊፎርኒያ እሳት አደጋ ኮማንደር ኬቪን ላውሰን በበኩላቸው፤  በማስተፈሻ ላይ የደረሰው ጉዳት በግድቡ ላይ ሊያደርሰው የሚችለው የመፍረስ አደጋ ስጋት አለመኖሩን አስታውቀዋል።

ማስትንፈሻዎቹ ላይ ከደረሰው እከል በተጨማሪ በግድቡ ላይ የተጋረጠ የመፍረስ ስጋት አለመኖሩም ተጠቁማል። ሎስ አንጀለስ ታይምስ እንዳስነበበው ከሆነም፤መስተንፈሻዎቹ ላይ የደረሰውን ጉዳት ዳግም ለመጠገን ከ100 እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር ወጪን ይጠይቃል።

ሰዎች አካባቢውን እንዲለቁ ትዕዛዝ ማስተላለፍ ያስፈለገበት ምክንያት የከፉ ነገሮች እንዳይከሰቱ ቀድሞ ከመስጋት መሆኑን የተጠቆመ ሲሆን፤አሁን ላይ የአደጋ ስጋቱን ሸሽተው የሄዱ ሰዎች ወደ ቀድሞ አካባቢያቸው ይመለሱ አይመለሱ የሚለውን ለማረጋገጥ ውሳኔ ላይ አለመደረሱንና የስጋቱ ደረጃም በሚመለከታቸው አካላት እየተመረመረ እንደሚገኝ  የቢቢሲ መረጃ አመላክቷል።

ካሊፎርኒያ ከረጅም ጊዜያት ድርቅ በኋላ በቅርቡ ከፍተኛ የሆነ ዝናብ በመጣሉ ምክንያት ከተማው ለጎርፍና ለመሬት መንሸራራት መዳረጉ ይታወሳል።

 

ታምራት ተስፋዬ

Published in ዓለም አቀፍ

የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የመገንባት ጉዳይ አገራዊ የጋራ ህልውናችንን የማስቀጠል አለማስቀጠል ጉዳይ እንጂ ምርጫ አይደለም የሚለው ፅኑ አቋም ዛሬም ድረስ ሊሰመርበት የሚገባ ነጥብ ነው። 

ላለፉት 25 ዓመታት በዚህች አገር ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ስለመከፈቱ ካስመሰከርንባቸው እውነታዎች መካከል ቀዳሚ ሥፍራ ይይዛል። የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ሲባል በኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በኩል ያልተቆጠበ ጥረት የተደረገበት እልህ አስጨራሽ ሂደት ነበር ቢባል ተገቢ ይሆናል። 

በዚህች አገር ሕዝቦች የጋራ ታሪክ ልዩ ሥፍራ እንደሚሰጠው በርካታ የውጭ ታዛቢዎች ሳይቀሩ የመሰከሩለት የፌዴራላዊት፤ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የደነገጋቸው ዓለም አቀፋዊ ደረጃቸውን የጠበቁ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አከባበር ድንጋጌዎች በየትኛውም መመዘኛ ቢለኩ እኛ ከምንለው ጋር የሚቃረን እውነታ መኖሩን አያመለክቱምና ነው፡፡

ይሁን እንጂ ግን ለዘመናት “ንጉስ አይከሰስ፤ ሰማይ አይታረስ” ከተሰኘው የገዥ መደቦች ኦሪታዊ ፈሊጥ በመነጨ በአፈና ሥርዓት ሥር ስትማቅቅ ለቆየችው አገራችን የ1983ቱ ታሪካዊ ድል ያመጣላትን ሥር ነቀል ለውጥና የለውጡ መገለጫዎች የሆኑትን ፈርጀ ብዙ ፋይዳዎችም ጭምር አምነው ላለመቀበል የተገዘቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ከትናንት እስከ ዛሬ የሙጥኝ ያሉት አቋም አሁንም ድረስ እያስገረመን ይገኛል፡፡

ይህን የምንለው ደግሞ በተለይም አንዳንድ ፅንፈኝነት የተጠናወተውን አስተሳሰብ የሚያቀነቅኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከዚያን ጊዜ አንስተው አሁንም ድረስ ሲያነሱ የሚደመጡትን "የብሔራዊ መግባባት" ጥያቄ ጉዳይ እኛ እንደምንረዳው ከሆነ፤ ገና ድሮ ምላሽ አግኝቷልና ነው፡፡ እስቲ ይህን መከራከሪያችንን በምክንያታዊ ማብራሪያ አስደግፈን ለማስገንዘብ እንሞክርና ከዚያ ፍርዱን ለአንባቢያን እንተወዋለን፡፡

በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ፅንፈኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ደጋግመው ስለሚያነሱት ጥያቄ የሚሰማንን መግለፅ እንዳለብን ያመንነው በተለይ አገራችን ኢትዮጵያ ለሁለተኛው አምስት ዓመት የትግበራ ዘመን የነደፈችውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አጠቃላይ ይዘት በተመለከተ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራር አካላት ጭምር ገምግሞ አስተያየት እንዲሰጥበት ሲባል መንግሥት ላቀረበላቸው ግብዣ "መጀመሪያ መቅደም ያለበት "አገራዊ መግባባት የመፍጠር ጉዳይ ነው" በሚል ሰበብ ግብዣውን ሳይቀበሉት የቀሩ ጥቂት ፓርቲዎች መኖራቸው የቅርቡ ትውስታችን ነው። 

እነዚሁ ኃይሎች በዚያን ወቅት ለአንዳንድ የግል ፕሬስ ሚዲያ ውጤቶች በሰጡት ምላሽ "በህዝብ ተመርጦ ሥልጣን ያልያዘ መንግሥት የነደፈውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እንድንገመግም ስንጠራ ከሄድን እኮ ለኢሕአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ እውቅና መስጠት ይሆንብናል" ሲሉ መደመጣቸውን ጭምር ስንታዘብ እነሆ ዛሬ በዚህ ጽሁፍ አንዳንድ መሠረታዊ የመከራከሪያ ነጥቦችን እያነሳን እንመለከት ዘንድ ወደናል፡፡

እንግዲያውስ በእኛ እምነት እነዚህ ፅንፈኛ ፓርቲዎች የተቃውሞው ጎራ ፖለቲካ ኃይሎች ዛሬ እንኳን ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ያቀረበላቸውን የአብረን እንስራ ግብዣ ተቀብለው የራሳቸውን ገንቢ አስተዋፅኦ የማበርከት አዝማሚያ ከማሳየት ይልቅ የሰማነውን ኢ ምክንያታዊ መከራከሪያ የሙጥኝ ማለታቸው ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ትዝብት ላይ ይጥላቸው እንደሁ እንጂ ሌላ ትርፍ አያስገኝም፡፡ በተለይም ደግሞ ኢሕአዴግን ሕዝብ ሳይመርጠው ሥልጣን የጨበጠ አምባገነናዊ አገዛዝ አድርጎ ለመፈረጅ መሞከር ትዝብት ላይ ከመጣል ያለፈ ኪሳራ ሊያስከትልባቸው እንደሚችል ለመገንዘብ ፖለቲከኛ መሆን አይጠይቅም፡፡

ምክንያቱም ኢሕአዴግ እልፍ አዕላፍ የትግሉ ሰማዕታት የወደቁለትን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የመገንባት መርህ ተግባራዊ ለማድረግ የሚታትረውን ያህል ተቃዋሚዎቹ የሚያሳዩት የነውጥ ናፋቂነት አዝማሚያ ባፈጠጠና ባገጠጠ መልኩ ገሃድ ወጥቷልና ነው፡፡

ስለዚህ እርስ በርስ ወደ መናቆር አደጋ ሊወስድ የሚችለውን የሥልጣን ናፋቂ ኃይሎች ጭፍን ተቃውሞ መስማት የሰለቻቸው የአገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ኢሕአዴግን እንደመረጡ ብቻም ሳይሆን ለምን እንደመረጡት ጭምር አሳምረው ያውቃሉ፡፡

ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ከመጀመሪያው አምስት ዓመት በተሻለ መልኩ ተግብረን፤ ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው የዓለማችን አገራት ተርታ እንድትሰለፍ ለማድረግ ሲባል ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችንም ጭምር ያሳተፈ የውይይት መድረክ ላይ እንዲገኙ በመንግሥት ሲጋበዙ የተለመደውን ተልካሻ ሰበብ አስባብ እንደ ቅድመ ሁኔታ በማቅረብ ግብዣውን ሳይቀበሉት ለቀሩ ቡድኖች ዛሬም ደግመው ደጋግመው ሊያውቁት የሚገባው ጉዳይ ቢኖር እነርሱ ኢሕአዴግን በፀረ ዴሞክራሲያዊነት ለመውቀስም፤ ለመክሰስም የሚያስችል የሞራል ብቃት እንደሌላቸው ነው፡፡

 መላው የአገራችን ሕዝቦች ፈርጀ ብዙ መስዋዕትነት ባስከፈላቸው የዘመናት ትግል የተቀዳጁትን የግንቦቱን ድል ተከትሎ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የመከፈቱን እውነታ አምኖ መቀበል "ለወያኔ ሥርዓት እውቅና እንደመስጠት የሚቆጠር ውርደት" መስሎ የሚሰማቸው ግብዝ ተቃዋሚዎች ደጋግመው ሲያመነዥኩት ከሚስተዋለው ጭፍን ተቃውሞ ወይም የጥላቻ ፖለቲካ ጋር መጋፈጥ ግድ ባልሆነ ነበር፡፡

በተለይም ደግሞ እነርሱ "ብሔራዊ እርቅ ማውረድ ያስፈልጋል" እያሉ ከትናንት እስከ ዛሬ ሥርዓቱን ለማጥላላት ሲሞክሩ የሚስተዋሉበት አግባብ ሲጤን ምን ያህል አስተዛዛቢና የማያቀባብርም ጭምር ሆኖ እንደሚገኝ መግለጹ ተገቢነት ይኖረዋል።

ምክንያቱም፤ ፅንፈኞቹ የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝነት አመለካከትን የሚያቀነቅኑ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች አሁንም ድረስ በቀጠለ ኩርፊያቸው ምክንያት፤ ፈርጀ ብዙውን የኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዞ ለመቀልበስ፤ አሊያም ደግሞ ለማጓተት ያለመ ሴራ መዶለትን የመረጡት "አገራዊ መግባባት ሳይፈጠር ስለልማት ማሰብ አይቻልም" በሚል ሰበብ እንደሆነ ይታወቃልና ነው፡፡

ስለዚህም እነርሱ የሚጠይቁትን ዓይነት "ብሔራዊ እርቅ" አሊያም ደግሞ "አገራዊ መግባባት" ገዥው ፖርቲ ኢሕአዴግ ሳይወድ ተገዶ እንዲቀበል ለማድረግ ሲባል፤ ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ መንግሥት የነደፋቸውን የልማት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በታቀደላቸው ጊዜ እንዳይሳኩ የማድረግ ዓላማ ይዘው ለመንቀሳቀስ እንደወሰኑ የሚያመላክት ድባብ ስለመኖሩ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡

ከዚህ አኳያም ነው፤ ይበጃል የሚባለውን ቀና መንገድ ሊጠቆምና መስማት ቢፈቅዱ እውነቱን ሊነገራቸው ተፈልጎ ይህ ርዕሰ ጉዳይ መነሳቱ። ስለሆነም ዛሬም ድረስ የተለመደውን ሰንካላ ሰበብ አስባብ እንደምክንያት እያቀረቡ የኩርፊያ ፖለቲካቸውን የሙጥኝ ያሉት አንዳንድ ፅንፈኛ ተቃዋሚ ቡድኖች አሁን እንኳን ወደ አዕምሯቸው ይመለሱ ዘንድ በአፅንኦት ልንገልጽላቸው እንሻለን፡፡

በተለይም እነርሱ መፈጠር አለበት እያሉ የሚናገሩለትን "አገራዊ መግባባት" ስንመለከተው ማንንም ሊያሳምን እንደማይችልና ከጥላቻ ፖለቲካቸው በሚመነጭ ግትር አቋም ለግብር ይውጣ የሚቀርብ ኢ ምክንያታዊ መከራከሪያ የመሆኑ ጉዳይ በፈጠጠና ባገጠጠ መልኩ ይገለጽልናል፡፡

ወጣም ወረደ ግን፤ የተቃውሞው ጐራ ጽንፈኛ ኃይሎችና ምዕራባውያን ኒዮ ሊበራል የእንጀራ አባቶቻቸው በተቀናጀ መልኩ የሚያቀነባብሩት ፀረ ኢሕአዴግ ሴራ ስላልተሳካ "በኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች መካከል እርቀ ሠላም ለማውረድ የሚያስችል አገራዊ መግባባት መፈጠር አለበት" የሚል መከራከሪያ ማቅረብ ተራ ብልጣ ብልጥነት ስለመሆኑ ነው ልናሰምርበት የሚገባን ነው ፡፡

እንዴት ቢባልም ተሸናፊዎቹ ቡድኖች ሕገ መንግሥቱን እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንም ጭምር እንደማይቀበሉትና በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ታግለው ሊያስወግዱት እንደሚፈልጉ ደጋግመው ሲናገሩ መደመጣቸው አልበቃ ብሎ፤ የአመፅ ስትራቴጂያቸውን መሠረት አድርገው የአዲሲቷ ኢትዮጵያን ሕዝቦች እርስ በርስ ለማናቆር የማይፈነቅሉት የጥፋት ድንጋይ አለመኖሩን ልቦናቸው ሲያውቀው ጭራሽ በእነርሱ ብሶ አገራዊ የጋራ መግባባት ስለመፍጠር ጉዳይ እንድናስቀድም ሊያሳስቡን መሞከራቸው በእርግጥም የለየለት ብልጣ ብልጥነት እንጂ ሌላ ስም ሊገኝለት አይችልምና ነው።

በመጨረሻም ከትናንቱ ተሞክሯችን ተነስተን ዛሬ በኢሕአዴግ እና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ውይይት በቀጣይም የሚደረገው ድርድርና ክርክር በሰለጠነና ጨዋ በሆነ መንገድ ፍጻሜ ያገኛል ብዬ አምናለሁ።

 

ወንድይራድ ኃብተየስ

Published in አጀንዳ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።