Items filtered by date: Wednesday, 15 February 2017

የሰሜን ኮሪያ ሚሳይል ሙከራ

በዛሬዋ ዕለት  እ.አ.አ የካቲት 8ቀን 1998 እና 1979 አሜሪካ ውጤታማ  የሚባሉ ሚሳይል የማስወንጨፍ ሙከራዎችን አድርጋ ነበር፡፡ ከ38 ዓመት በኋላ ሰሜን ኮሪያ የተባበሩት መንግሥታት ያስቀመጠውን ሚሳይል የማስወንጨፍ ሙከራ ማዕቀብ ስምምነትን በመጣስ እኤአ የካቲት 12ቀን2017  ፕሬዚዳንት ትራምፕ ስልጣን ከያዙ ወዲህ የመጀመሪያውን ሚሳይል የማስወንጨፍ ሙከራ ማድረጓን ቢቢሲ የዜና ማሰራጫ አውታር ዘግቧል፡፡

በሰሜን የኮሪያ ልሳነ ምድር ፒዮንጋንግ ግዛት አየር ጣቢያ በኪም ጆንግ መሪነት  እንዲወነጨፍ የተደረገው ሚሳይል ስኬታማ በሆነ መልኩ ወደ ጃፓን ባህር አቅጣጫ 500 ኪሎ ሜትር አካባቢ አምዘግዝጎ ማረፉን ደቡብ ኮሪያ ገልፃለች። የአሁኑ የሰሜን ኮሪያ የባሊስቲክ ሚሳይል ሙከራ በተለያዩ አገራት ውግዘት አስከትሎባታል። አሜሪካን፣ ጃፓን፣ ቻይና እና ደቡብ ኮሪያ ለተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት በማድረግ ድርጊቱን አውግዘውታል፡፡

 ሀገራቱም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የሰሜን ኮሪያን የሚሳይል ሙከራም ድርጊት እንዲሁ አውግዞታል። የኔቶ ዋና ፀሃፊ ጀንስ ስቶተንበርግ ፒዮንግያንግ ውጥረት ከመፍጠር እንድትቆጠብ እና ከአለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጋር ውጤታማ ውይይት እንድታደርግ አሳስበዋል።

የአውሮፓ ህብረትም ሙከራውን ያወገዘ ሲሆን፥ ሀገሪቱ አለም ዓቀፍ ግዴታዎችን በተደጋጋሚ መጣሷ ፀብ አጫሪነት ያለው ተግባር  ነው፤ ይህም ተቀባይነት የለውም ብሏል።

 በተመሳሳይ ትራምፕ ድርጊቱን አውግዘው እንደዚህ አይነቱን ድርጊት አንታገስም ብለዋል፡፡ የፒዮንያንግ ሚሳይል ማስወንጨፍ ለአዲሱ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ትልቅ ፈተና መሆኑን ተንታኞች እየገለፁ ይገኛሉ፡፡የአሜሪካው ፕሬዚዳንትም ከጃፓን ጎን እንደሚቆሙ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡ ሚስተር ትራምፕ ለጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሺንዞ አቤ እንዳረጋገጡት “አሜሪካን ከጃፓን ጎን ትቆማለች ፡፡ ትልቅ አጋሯም ትሆናለች ፡፡መቶ በመቶ “ብለዋል፡፡

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እሁድ ዕለት  በተደረገው የሚሳይል ሙከራ መደሰ ታቸውን የገለጹ ሲሆን፥ ሙከራው “የሀገሪቱን ጥንካሬ የሚጨምር ነው” ብለዋል። የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር ፒዮንግያንግ የሚሳይል ትንኮሳ ሙከራውን ያደረገችው አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጉዳዩ ላይ የሚሰጡትን ምላሽ ለማድመጥ  ነው ብሏል።

            ባለፈው ጥር ወር የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጦራቸው ረዥም ርቀት የሚጓዝ ሚሳይል ለመሞከር እንደተቃረበና አሜሪካም መድረስ እንደሚችል ተናግረው ነበር ፡፡ሚስተር ትራምፕ በቲውተር ገፃቸው እንዳሰፈሩትም ድርጊቱን “ሊሆን የማይችል “ሲሉ በቁጣ መግለፃቸው የሚታወስ ነው ፡፡

የባሊስቲክ ሚሳይሉ ምድር ለምድር ከመካከለኛ እስከ ረጅም ርቀት የሚምዘገዘግ ነው ተብሏል። የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ የዜና ወኪል ኬ ሲ ኤን ኤ እንደዘገበው፥ይህን የተሳካ ነው የተባለለት የሚሳይል ሙከራ “ፑክጉክሶንግ 2” የተሰኘው ሚሳይል ኒዩክሌር መሸከም ይችላል ተብሏል።

ይህ የአገሪቱ የሚሳይል ሙከራ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሁለተኛው ሲሆን በተያዘው የፈረንጆች ዓመትም ስድስተኛው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ከኒውክሊየር መርሃ ግብሯ ጋር በተያያዘ ከምዕራባውያን ጋር ውዝግብ ውስጥ የምትገኘው ፒዮንግንግ መርሃ ግብሯን ከማቋረጥ ይልቅ አጠናክራ መቀጠሏን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 ለሁለተኛ ጊዜ ተደርጎ የነበረው  የሚሳይል ሙከራ ስኬታማ ሳይሆን አየር ላይ ተበታትኖ እንደቀረ ይታወሳል፡፡ ሮዶንግ; የሚባለው ሚሳይል እስከ 1300 ኪሎ ሜትር ያህል የመወንጨፍ ብቃት አለው ተብሎ ቢጠበቅም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ የሚሳይል ሙከራውን ተከትሎ አሜሪካ ሰሜን ኮሪያ ከጸብ አጫሪ ድርጊቷ እንድትቆጠብ አስጠንቅቃ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የወቅቱ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሰሜን ኮሪያ ዓለም አቀፉን ህግ በሚጻረር መልኩ የኒውክለር ሙከራ በማድረጓና ሳተላይት በማስወንጨፏ አዲስ ማዕቀብ ሀገሪቱ ላይ መጣላቸውም ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትም በሙሉ ድምፅ ድርጊቱን ማውገዙንና የዓለም አቀፍ ህግ ተላልፋለች በሚል በአይነቱ ከባድ የተባለለትን ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።

ፒዮንግያንግም ዋሽንግተን ማዕቀቡንና ሌሎች በአገሪቱ ላይ የምታደርጋቸውን ትንኮሳዎች ካላቆመች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ሙሉ ለሙሉ ለማቋረጥ እንደምትገደድ ማስጠንቀቋን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቶ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

 እአአ ሃምሌ1ቀን2008 አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ የሚሳይል መከላከያ ሃይል ለማሰማራት መስማማታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ስምምነቱ ደቡብ ኮሪያ ከሰሜን ኮሪያ የሚሰነዘርባትን የጠብአጫሪነት ትንኮሳ ለመመከት ያለመ መሆኑን መገለፁ የሚታወስ ነው፡፡ ዘ ተርሚናል ሃይ አልቲቲዩድ ኤሪያ ዲፌንስ/THAAD/ የተሰኘው የሁለቱ አገራት የጸረ ሚሳይል ሃይል  የሚሰማራበት ትክክለኛ ቦታና ማን እንደሚቆጣጠረው ከሁለቱም ወገን ግልጽ መረጃ እንዳልተሰጠ ነው ቢቢሲ የዘገበው፡፡

ፒዮንግያንግ ባለፈው ዓመት በዚሁ ወር የረጅም ርቀት ሚሳይል ማስወንጨፍ ሙከራ ማድረጓን ተከትሎ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ በጉዳዩ ዙሪያ ሲመክሩ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ሁለቱ ሀገራት አሁን በደረሱበት የሚሳይል መከላከያ ስምምነት መሰረት የሚሰማራው ትሃድ የተባለው ሃይል ከፒዮንግያንግ በኩል የሚሰነዘርን የተወንጫፊ ሚሳይል ጥቃት ማክሸፍ የሚችልና ሚሳይሎችን አስቀድሞ መከላከል የሚችል ነው ተብሏል፡፡

ፒዮንግያንግ ይህን ማስጠንቀቂያም ሆነ ማስፈራሪያ ከእቁብም ሳትቆጥረው እኤእ  ነሀሴ 4ቀን 2016 ዓ.ም የባላስቲክ ሚሳይል ሙከራ አድርጋለች፡፡ አገሪቱ ያስወነጨፈችው ሚሳይል በጃፓን ግዛት በሚገኝ ባህር ውስጥ መውደቁም ይታወሳል፡፡ ሚሳይሉ 1 ሺህ ኪሎ ሜትር መምዘግዘግ የሚችል እንደሆነም የደቡብ ኮርያ እና ጃፓን  በወቅቱ አስታውቀዋል፡፡ ፒዮንግ ደቡብ ኮርያ እና አሜሪካ የመከላከያ ሚሳይሎችን ለመትከል እቅድ መንደፋቸውን ተከትሎ የጦር መሳሪያ ፍተሻዋን አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን ማስታወቋ ይታወሳል፡፡ የጦር መሳሪያ ፍተሻው አገሪቱ አጎራባቾቿ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ያላትን ፍላጎት ያሳያል ሲሉ የደቡብ ኮሪያ እና የጃፓን መንግሥታት አስታውቀዋል፡፡

የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ስምምነቱ ከሰሜን ኮሪያ ሊሰነዘር የሚችልን ጥቃት ለመከላከልና በአገሪቱ አስተማማኝ የጸጥታ ዋስትናን ለማረጋገጥ መሆኑን ገልፀው ፤ የሚሳይል መከላከያ ሃይሉም በፍጥነት ወደተግባራዊ ስራው እንደሚሰማራ የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር መግለፃቸው የሚታወስ ነው፡፡

 

 

Published in ዓለም አቀፍ
Wednesday, 15 February 2017 19:28

አገራቸውን ያኮሩ ተከበሩ

የ«ኢትዮጵያ ፈርስት ዶት ኮም» ዘጋቢ ፊልም የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በሶማሊያ  ሀልጌን ሰኔ 2 ቀን 2008 ዓ.ም ያደረገውን አኩሪ ተጋድሎ አቀናብሮ ለዕይታ አቅርቧል። በዘጋቢ ፊልሙ መረጃ መሰረትም፤ የተጠቀሰው ቀን ጎህ ሊቀድ በተቃረበበት ሰዓት የአሸባሪው አልሻባብ ተዋጊዎች በኢትዮጵያ የደቡብ ምስራቅ ዕዝ 13ኛ ሻለቃ 4ኛ ሪጅመንት የጦር ሰፈር ላይ ያልታሰበ ጥቃት ሰነዘሩ።

ድንገት ጥቃት የተቃጣበት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትም ጥቃቱን ቀልብሶ እስከ ረፋዱ አራት ስዓት ድረስ ጀግንነት የተሞላበት ውጊያ አድርጎ አልሸባብን ሙሉ ለሙሉ በመደምሰስ ግብዓተ መሬቱን እዛው ፈጽሟል።

ትላንት አምስተኛው የመከላከያ ሰራዊት ቀን በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ “በህዝባዊ መሰረት የተገነባው ጀግንነታችን እየታደሰ ይኖራል” በሚል መርህ ሲከበር በአልሸባብ የተሰነዘረበትን ጥቃት በከፍተኛ ወታደራዊ ብቃት የመከተችው ይህችው ሪጅመንት፤ በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት አዋጅ ቁጥር 809/2006 መሰረት በማንኛውም አውደ ውጊያ የላቀ የጀግንነት ስራ ላከናወኑ አካላት ሽልማት እንደሚሰጥ ተደንግጓልና ተሸላሚ ሆናለች። ሽልማቱም ሁለተኛ ደረጃ የምስክር ወረቀትና የጀግንነት ሜዳሊያ እንደሆነ ተገልጿል።

በዕለቱ ንግግር ያደረጉት የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሀመድ፤ አልሸባብ በኢትዮጵያ ላይ ጅሃድ አውጆ ጥቃት ለመሰንዘር ሲንቀሳቀስ ከሶማሊያ ተዋሳኝ የሆነው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በሽብር ቡድኑ የመጀመሪያው ተጠቂ ሊሆን ይችል እንደነበር አንስተው፤ «የመከላከያ ሰራዊታችን አልሻባብ እስካለበት ሄዶ ባለበት  በመደምሰስ እንዲቆም በማድረጉ የክልሉ መንግሥት ምስጋና ያቀርባል» ብለዋል።  

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻም፤ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አሸባሪዎች የሚሰነዝሩበት ተደጋጋሚ ጥቃት ለልማቱ እንቅፋት ሆኖበት ቆይቷል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት በክልሉ ይንቀሳቀሱ የነበሩ አሸባሪዎችን ማጥፋት ችሏል። ታንክ ጭነው ሲሄዱ የሚታወቁት የሎቤድ መኪኖች ዛሬ ላይ ልማት የሚያፋጥኑትን ዶዘር፣ ትራክተርና ኤክስካቫተርን እያጓጓዙ ናቸው። የክልሉ ህዝብም መከላከያ ሰራዊቱ ላመጣው ሰላም ልዩ የሆነ ክብር አለው።

የኢፌዴሪ መከለካያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሳሙራ የኑስ በበኩላቸው፤ ሰራዊቱ ከህዝብና ከመንግሥት የተሰጠውን አደራ በመቀበል የሻዕቢያ ተላላኪዎችን፣ ዓለም አቀፍ አሸባሪዎችንና የውስጥ የጸጥታ ችግር ፈጣሪዎችን ተከታትሎ በማምከን አኩሪ ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል።

«በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖርና ሶማሌያውያን ወንድሞቻችን ወደ ልማት እንዲገቡ ለማድረግ ሰራዊታችን በአሚሶምና ከአሚሶም ውጭ አሸባሪዎችን በማጽዳት አኩሪ ጀብዱና ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። በሶማሊያ ሀልጌሳ ከተማ የ13ኛ ሻለቃ 4ኛ ሪጅመንት አልሸባብን በመምታት የሞራልና የቁስ ኪሳራ አድርሷል። የሰራዊታችን የቀድሞ ጀግንነት አሁንም እንዲቀጥል በማድረግ ግዳጁን ፈጽሟል። ለዚህ አኩሪ ድልና የሪጅመንቱ አባላት ለፈጸሙት አኩሪ ጀግንነት በውጊያው ለተሰውና በህይወት ላሉ የምስክር ወረቀትና የክብር የኒሻን ሚዳይ አበርክተልናቸዋል" ብለዋል ጀነራል ሳሞራ ።     

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፤ ኢትዮጵያ የዓለምን ሰላም ለማስከበር ክጥንት ጀምሮ እስካሁን በተለያዩ አገራት አኩሪ ውጤት አስመዝግባለች። አገሪቱ የዓለም ሰላምን ለማስከበርም ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍላለች። ባደረገችውም መስዋዕትነት በዓለም አገራት ተቀባይነት አግኝታለች። በተለይም ሰላም አስከባሪዎቿ በተሰማሩበት አገር ሁሉ ህዝባዊነታቸው፣ ሰብዓዊነታቸው እና ጀግንነታቸው የተመሰከረላቸው መሆናቸው የሚያኮራ ነው ብለዋል።

«በጎረቤታችን ሶማሊያ የአልሸባብ አሸባሪ ቡድን ሶማሊያን በመቆጣጠር የአገራችንን ሰላምና ልማት ከውስጥ ጸረ ሰላምና ጸረ ልማት ሀይሎች ጋር በመቀናጀት ሰላማችንና ልማታችን ለማደናቀፍ ብሎም ቀጣናውን ለማተራመስ ያደርግ የነበረውን ሴራ ከአፍሪካ ህብረትና ከሶማሊያ መንግሥት በቀረበው ጥሪ መሰረት በግልና በህብረቱ ሰራዊት ውስጥ በመታቀፍ  መከላከያ ሰራዊታችንን  እስካለበት ሄዶ እንዲከስም ማድረጉ ለአገራችንም ሆነ ለቀጣናው ሰለም ትልቅ ድል ነው» ሲሉም ነው የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻም፤ በሀልጌሳ ከተማ ከአንድ ሺ በላይ የአልሸባብ ተዋጊዎች በመሳሪያና በተለያየ መልኩ ዝግጅት በማድረግ በሰራዊታችን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሲሞከሩ ከአባቶቹ የወረሰውን የአገር ሉዓላዊነት የማስከበርና የአልደፈርም ባይነት መንፈስ ተላብሶ የአገሩን ክብር አስጠብቋል። የተቋማቸውን እሴት ሙሉ በሙሉ በማክበርም መከላከያ ሰራዊቱ እየተጠናከረ መጥቷል። ይህ የቀድሞውን የአገርና የህዝብ አደራን ይዞ በምንም እና በማንም አልደፈርም የሚልውን ዓለማ ያስቀጠለ ነው። ይህ ዓለማ ቀጣይ እንዲሆን መንግሥት ጥረት ማድረጉን ይቀጥላል። 

 

ዜና ሐተታ

አጎናፍር ገዛኽኝ

Published in የሀገር ውስጥ

ብርሃኑ ተሰማ የተባለ ጸሀፊ ከዚህ በታች ያለውን ጽሁፍ አስፍሮ አገኘሁ። እኔም በጥቂቱ ተዋስኩና እንዲህ አድርጌ አቀረብኩት። (የጽሁፉን ምንጭ ተናገርኩ ማለት ነው) ጊዜው 1975 ዓ.ም ነበር።  የዛሬውን አያድርገውና ሊቢያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) የመሪዎች ጉባዔን ለማስተናገድ ሽርጉድ ከጀመረች ውላ አድራለች። በተቃራኒው ኃያሏ አገር አሜሪካ ግን በፕሬዚዳንቷ ሮናልድ ሬገን አማካይነት ጉባዔው እንዳይሳካ ጥረት ማድረግ ጀመረች። ሊቢያንና መሪዋን አሸባሪ በማለትም ጉባኤውን በተደጋጋሚ አስተጓጎለችው።

ከአንዴም ሁለቴ በአሜሪካ በአሸባሪነት በተፈረጀችው አገር እንዳይካሄድ የተፈረደበት ጉባዔ መጨረሻ ላይ ወደ ትውልድ አገሩ ይሂድና ጉባዔው ይካሄድ የሚል ውሳኔ ተላለፈበት። አ.አ.ድን የወለደችው አዲስ አበባም በአስቸኳይ መሪዎቿን ጠርታ ጉባኤውን አስተናገደች። የአገሪቱ መሪ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምም የዓመቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ።

በወቅቱ የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሼሁ ሻጋሪ ለኢትዮጵያ ሬዲዮ፤ "ድርጅቱ ወደተወለደበት አገር ሲመጣ ከሕመሙ ተፈወሰ’’ ሲሉ መናገራቸው ዛሬም ድረስ ይታወሳል፤ ሲል በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት ጸሀፊ ታሪኩን ነግሮናል።

  ይህ የኢትዮጵያ ለአፍሪካ ችግር ሁሉ ቀድሞ የመገኘት ታሪኳ ከዘመን ዘመን፤ ከመንግሥት መንግሥትም እየተጠናከረ ሲመጣ እንጂ ሲቀንስ አልታዬም። (ቆየት ብዬ በደርግ ዘመን መቀዛቀዙን ስጠቅስ እንዳይታዘቡኝ ከወዲሁ አደራ)  በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የማትመክርበት፣ የማትጋበዝበት የማትሰማራበትም የአፍሪካዊያን ችግር ያለ ሁሉ አይመስልም።

በተለይም በሰላም ማስከበርና በቅኝ ግዛት ስር ሲማቅቁ ለነበሩ አገራት ያደረገችው ድጋፍ አሁንም ድረስ የዘለቀው ታሪኳ ቢነገር ቢነገር የማይሰለችም ብቻ ሳይሆን የማይጠገብም ጭምር ነው። ለዚህም  ነው ኩራታችን ራታችንም ማለቴ። 

አገራችን በቅኝ አገዛዝና በአፓርታይድ ሥርዓት ሲሰቃዩ የነበሩ አፍሪካውያን የሞራል፣ የዲፕሎማሲና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ አገራቱ ነጻነታቸውን እንዲጎናጸፉ ያደረገችው አስተዋጾ ጉልህ ታሪኳ ነው። የእኛም ኩራታችን። በተለይም ለደቡብ አፍሪካ፣ ለናሚቢያና ለዚምባብዌ የነጻነት ትግል ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት ጭምር ያደረገችው አስተዋጽኦ ለራሳቸው ለአገራቱና ለእኛም ብቻ ሳይሆን ለተቀረው አፍሪካዊም ኩራት ነው።

ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር በኩል ታሪክ ማጻፍ የጀመረችው በኮሪያ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ይነግሩናል። ኮሪያዊያን በአገራቸው ተቃጥቶባቸው በነበረው ወረራ የሚገቡበት ጠፍቷቸው፤ ቀኑ በጨለመባቸው ሰማዩም በተደፋባቸው ወቅት ቀድመው ከደረሱ አገራት መካካል አገራችን መሆኗን ስናስብ እጅግ የሚያስገርም ታሪክ ሆኖ እናገኘዋለን። ምክንያቱም በዚያ ጨለማ ዘመን ብዙ ሺህ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ላለች አገር የድረሱልኝ ጥሪ፤ ከጨለማዋ አህጉር ፈጥኖ መልስ መስጠት ዛሬ ላይ ሆነን ስናስበው ህልም እንጂ እውን ላይመስል ሁሉ ይችላል።

ኢትዮጵያና ኢትዮጰያዊያን ግን ነጸነትንና ጥቅሙን አጣጥመው የሚያውቁ ህዝብና አገር ናቸውና ለኮሪያዊያን ጥሪ ቀድመው ደርሰዋል። ቃኘው ሻለቃ የተባለው ጦራችንም ከሌሎች 16 አገራት ወታደሮች ጋር በመሆን እጅግ አኩሪ ታሪክ ፈጽሞ ተመልሷል። ይህ የኢትዮጵያ ጦር የሚያስገርመው በኮሪያ በፈጸመው ጀብዱም ብቻ  ሳይሆን አንድም የህይወት መስዋዕትነት አለመክፈሉም ጭምር ነው።  በወቅቱ ሦስት ሺህ 518 የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት በሶስት የተለያዩ ዙሮች የተሳተፈ ሲሆን፤ 238 ውጊያዎችን በማድረግም ዓለም አቀፋዊ ወታደራዊ ግዳጁን መወጣት ችሏል። ከዚህ በላይ ኩራት ይኖር ይሆን? ለእኔ በጭራሽ።

በኮንጎ የተደረገው የሰላም ማስከበር ስራም ቀጣዩ የአገራችን የዓለም ሰላም ዘብነት ታሪክ የተጻፈበት አጋጣሚ  ነበር። የቤልጂዬም ጦር ኮንጎ ላይ በማን አለብኝነት ጥቃት በመሰንዘሩ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ፓትሪስ ሉሙምባ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት  የድረሱልኝ ጥሪ ያቀርባሉ። ድርጅቱም ይሄንን ተከትሎ ባደረገው ጥሪ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት አሁንም ቀድሞ በመድረስ ለኮንጎዎች የሰላምና የነጻነት ዘብ ሆኖ ተመልሷል።

ይሄኛው ጦር ደግሞ “ጠቅል” በሚል ስያሜ የዘመተና ኮንጎ በገባ በአጭር ጊዜ ውስጥም በተሰጠው ቀጣና ሰላምና መረጋጋትን ማረጋገጥ የቻለ ጀግና ጦር ነበር። በእርግጥ ኢትዮጵያ ገና ማልዳ ለሌሎች አገራት ሰላም ፈጥና የመድረስ ታሪኳ የደርግ ስርዓት ከመጣ በኋላ ተኮላሽቷል። በእርግጥ በደርግ ዘመንም ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ለእንደ ደቡብ አፍሪካና ናምቢያ ያሉ አገራት ነጸናት ትግል ያበረከተው አስተዋጽኦ አይካድም። ሆኖም ከሰላም ማስከበር አንጻር ግን ደርግ  የሚጠቀስ ታሪክ መስራት ሳይችል ቀርቷል።

እዚህ ላይ አንድ ነገር ጠቅሼ ልለፍ። እንዳልኩት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር በንጉሱ ዘመን ወደር የሌለው እንደነበር ታሪኩ ይነግረናል። ደርግም ቢሆን ለተጠቀሱት አገራት የነጻነት ትግል ያደረገው ድጋፍ አይካድም። ነገር ግን "የውጭ አልጋ የውስጥ ቀጋ" እንዲሉ የሁለቱም መንግሥታት ወታደሮች በውጭ አገራት ዘንድ የሚነገር ታሪክ ቢፈጽሙም በአገር ውስጥ ግን ወታደሮቻቸው የሰላም ዘብ፤ የልማት ሀይል ከመሆን ይልቅ ህዝቡን የሚያስሩ፣ የሚገድሉና የሚያሰቃዩ እንደነበሩ መዘንጋት የለበትም። ለውድቀታቸውም መንስኤ የሆነው ይሄ ህዝባዊ ያልሆነው ባህሪያቸው ነው።

ወደ ሰላም ማስከበሩ ታሪክ ልመለስ።

ከንጉሱ ዘመን በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው ደርግ እንኳንስ ለሌሎች አገራት ሰላም ሊተርፍ ይቅርና ለአገር ውስጥ እንኳን የሚሆን ሰላምን ማምጣት ተሳነው። የተዛባው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውም ከአየአቅጣጫው ጠላት እንጂ ወዳጅ ሊያፈራለት አልቻለም። ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ግብጽና ሌሎች አገራት ደርግን በግራና በቀኝ ወጠሩት፤ ቁም ስቅሉንም አሳዩት። በውስጥም ነጻነትና ዴሞክራሲ ናፋቂ ወጣቶች ደርግን ሰቅዘው ያዙት። ወታደራዊው መንግሥትም "ሁሉም ነገር ወደጦር ግንባር" ወደ ሚል የሞኝ መርህ ተዘፈቀና አረፈው።

የሌሎች የነጻነት ቀንዲል የሰላምም ዘብ የነበረችው አገር ሰላሟ ጠፋ፤ ልማቷ የኋልዮሽ ሆነ። ልጆቿ ስደትን አንደኛ አማራጫቸው አደረጉት። የውጭ ግንኙነቷም ሻከረ፡፡ ስርዓት አልበኝነት ነገሰ። ማንም በሰላም ወጥቶ ስለመግባቱ እርግጠኛ መሆን አቃተው።

በዚህም ምክንያት ለ30 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያ ከሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውጭ ሆነች። ይህ ሁኔታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተቀየረው፤ የደርግ ስርዓት በቁርጥ ቀን ልጆች ከተወገደና ግብአተ መሬቱ ከተፈጸመ በኋላ ነበር። ኢትዮጵያ ወደነበረችበት የሰላም ማስከበር ታሪክ ለመመለስ ቅድሚያ ያደረገችው የተዛባውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መቀየር ነበር። አደረገችውም። በዚህም ሰላሟ ተመለሰ፤ ልማቷም መቀጣጠል  ጀመረ።

በዘህ መሀል ወንድም የሩዋንዳ ህዝብ ሰላሙ መጥፋቱ እርስ በርስም መገዳደል ጀመረ። ይሄ ጉዳይ ያሳሰበው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደተለመደው የሰላም ማስከበር ጥሪ ሲያደርግ ኢትዮጵያ ቀድማ አለሁ አለች። በድርጅቱ የፀጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ቁጥር 40 መሠረትም የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ሃይል በ1986 ዓ.ም ሩዋንዳ ተሰማራ። ልብ ይበሉ፤ በ1986 ነው ያልኩት።

ይህ ወቅት ገና መንግሥት ከተመሰረተ የሶስት ዓመት እድሜ ብቻ መቆጠሩ ነበር። አገራችን ግን ለሰላም ያላት ዋጋና አመለካከት ላቅ ያለ ስለሆነ ገና ከተመሰረተ ሶስት ዓመት እንከን ያልሆነዉ የሽግግር  መንግሥት ሰላም አስከባሪ ጦር ለሩዋንዳ ለመላክ አላቅማማም። ይሄ መከላከያ ሰራዊታችን ያጎናጸፈን ኩራታችን ነው። ያውም ደረት የሚያስነፋ።

ወደ ሩዋንዳ የተሰማራው ሰራዊታችንም በሁለት ዙር ተልዕኮውን በአስተማማኝ መንገድ ተወጣ፡፡ ሰራዊቱ በጥሩ ስነምግባር ከመታነጹም በላይ ለአካባቢው ህዝብ በሚያደርገው የተለያየ እገዛና በሚያሳየው ፍቅር የማይዘነጋ ታሪክ አጽፎ መምጣቱን የሩዋንዳን ታሪክ በቅርበት የሚያውቁት ሁሉ የመሰከሩት ሀቅ ነው።

ሩዋንዳ ዛሬ በአፍሪካም ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ከሚያስመዘግቡ እንደ ኢትዮጵያ ካሉ አገራት ተርታ መሰለፍ ችላለች። ይህ የሩዋንዳዊያን ስኬት ለእኛ ኩራታችን ነው። ሩዋንዳዊያንም በወቅቱ ላደረግልናቸው ሁሉ ምስጋናቸውን የአገሪቱን ከፍተኛ ሜዳሊያ ለታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ በመሸለም ገልጸውልናል። ይሄ አሁንም ኩራታችን ነው።

የኢትዮጵያ ቀጣዩ የሰላም ማስከበር ታሪክ የሚመዘዘው ደግሞ ከወደ ብሩንዲ ነው። በብሩንዲ መንግሥትና በአማጺያኑ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ሰምምነት በመጣሱ፤  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲሰማራ ይወስናል። ኢትዮጵያም እንደተለመደው አንድ ሺህ ሰራዊቷን ወደ ቡርንዲ አሰማራች፡፡ ሰራዊቱም የተሰጠውን አገራዊና አህጉራዊ ሃላፊነት በተገቢው መንገድ ተወጥቶ ኩራትም አላብሶን ተመልሷል።

ላይቤሪያ ቀጣይዋ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት የተሰማራባትና የተጠቀመች አገር ናት። አሁንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በላይቤሪያ ለተሰማራው ጦራችን የተኩስ አቁም ስምምነቱን መፈፀሙን መቆጣጠር፣ ትጥቅ ማስፈታትና ሰላምን ማረጋገጥ የሚል ሃላፊነት ሰጥቶት በአግባቡ ተወጥቶም ወደ አገሩ ተመልሷል።

በወቅቱም የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ሃይል ከ13 ሺህ በላይ አማጺያንን ትጥቅ በማስፈታትና ከ21 ሺህ 629 በላይ ስደተኞች ወደ ቀያቸው አንዲመለሱ ማድረግ ችሏል። በአገሪቱ ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድም የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ዛሬ ሁላችንም እንደምናውቀው ላይቤሪያ ያላችበት ሰላምና ልማት ላቅ ያለ ነው። ከዚህ ሰላምና ልማት በስተጀርባ ደግሞ እኛ አለን። ይሀ ታሪክ ሌላው በመከላካያ ሰራዊታችን ያገኘነው ኩራታችን ነው። 

የመከላከያ ሰራዊታችን አኩሪ ታሪክ ቀጥሎ በሶማሊያና በሱዳንም ያበረከትነውና እያበረከትን ያለነው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የጣሉበት አደራና ያሳደሩበት እምነት ደግሞ ከምንም በላይ ነው። አገራቱ በሚወዛገቡባት የአብዬ ግዛት ውስጥ የማንንም አገር ጦር አንፈልግም፤ ኢትዮጵያ ብቻ ብለው መርጠውን መግባታችን የሰራዊታችንን ህዝባዊነት ያረጋገጠ ነው።

በተለይ ደግሞ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ መንግሥት አልባ ሆና በኖረችው ሶማሊያ የመከለከያ ሰራዊታችን የፈጸመውና እየፈጸመ ያለው ገድል ታላቅነት የሰራዊቱን ታላቅነት የሚመሰክር ነው። ሰራዊታችን በሶማሊያ የገባው አንድም ለሶማሊያዊያን ወንድሞቻችን ሰላም ሲል ነው። ሌላም ለራሳችን ዘላቂ ሰላም እንደሆነ ከተልዕኮው ጀርባ ያለው ታሪክ ይነግረናል።

ሰራዊታችን ሶማሊያ ባይገባ ኖሮ ትላንት የእስላማዊ ፍርድቤቶች ህብረት፤ ዛሬ ደግሞ የአልሸባብ መቀለጃ መሆናችን አይቀርም ነበር። ነገር ግን ምስጋና ኩራትም ራትም ለሆነው ሰራዊታችን ይሁንና ይሄ አልሆነም። ኢትዮጵያ ሽብርተኞችን የምታስጎመጅ እንጂ የምትቀመስ አገር አልሆነችም። ይሄ የጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ውጤት ነው። ዛሬ አገራችን ስራ ላይ ናት። ከስራችን ጀርባ ያለው ደጀናችን ሰለማችን ነው። የሰለማችን ዘብ ደግሞ አሁንም መከላከያችን ነው። ይህ የህዝብ ልጅ የሆነ መከላከያ በአህጉርና በዓለም ደረጃ በታሪኩና በጀግንነቱ ኩራትን ሲያላብሰን፤ በአገር ውስጥ ደግሞ ልማትን እንድናጣጥም ስላደረግን ራታችንም ሆኗል።

እነሆ ትላንትም በጅግጅጋ ከተማ የሰራዊታችን ቀን ተከብሯል።  “በህዝባዊ መሰረት የተገነባው ጀግንነታችን እየታደሰ ይኖራል" በሚል መሪ ቃል  በተከበረው አምስተኛው የመከላከያ ቀን ላይ የተነገረው የሰራዊታችን ገድልም እጅግ አኩሪ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በተገኙበት በዚህ በዓል ላይ ሰራዊታችን ደምቆ ውሏል። ይህ ቢያንሰው እንጂ የሚበዛበት አይደለም። የሰራዊቱ አባላት የአልሸባብን ቅስም በመስበር ላደረጉት ተጋድሎም የክብር ሽልማት በመቀዳጀታቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የመከላከያ ሰራዊቱ ለማንም የማይበገር ሰራዊት ሆኖ እንዲቀጥል መንግሥት የሚያደርገውን ጥረትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

እኔም የምለው ይሄንኑ ነው። መንግሥት በዓመቱ መጀመሪያ  ላይ ለዚህ የህዝብና የአገር ዘብ ለሆነው ሰራዊት አድርገዋለሁ ያለው የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ በአፋጣኝ ይደረግለት። ትላንት  የህይወት መስዋዕትነት ጭምር ከፍሎ ይሄን አገር ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሯል። ሚሊዮኖችንም የልማቱ ተቋዳሽ አድርጓል። ዛሬ ደግሞ ተራው የእርሱ ነው። በደሙና በላቡ የገነባት አገር መልሳ የላቡንም ሆነ የደሙን ልትከፍለው ጊዜው አሁን ነው፡፡  ስለሆነም እላለሁ ኩራትም እራትም ለሆነን ሰራዊታችን ብድሩን እንክፈለው። አበቃሁ።

 

አርአያ ጌታቸው

Published in አጀንዳ

የኢትዮጵያ ህዝቦች በነፃነትና ልዑላዊነት ቀናኢነታቸው ወደር የሚገኝላቸው አይደሉም፡፡ አንድነትን፣ ሀገርን፣ ሰንደቅንና ነፃነትን ላለማስደፈር ለዘመናት በጀግንነት ሲወድቁ የኖሩትም በዚሁ ጠንካራ ማንነታቸው ነው፡፡ ሀገራችንን ከበርካታ ዓመታት በፊት አንስቶ የወረሩ የውጭ ኃይሎችን አይቀጡ ቅጣት እየቀጡ፤ ለአሁኑ ትውልድ ያስረከቡትን አያት ቅድመ አያቶቻችንን ለዘመናት ስንዘክር የመኖራችን ሚስጥርም ይሄውና ይሄው ብቻ ነው፡፡

አዲሲቷ ኢትዮጵያም ብትሆን ጥላትም ሆነ ጀግናና አርበኛ ትውልድን ያጣች አይደለችም፡፡ በተለይ ባለፉት 25 ዓመታት የሀገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በእኩል ተጠቃሚነትና ተሳትፎ እየገነቧት ያለችው ሀገራችን ዘላቂ ሠላሟን ያረጋገጠችው ታሪክ በተረከበው የመከላከያና የፀጥታ ኃይሉ ትጋት መሆኑ ሊዘነጋ አይችልም፡፡ የጀግኖቹ ወላጅ  የሆነው ህዝቡም ሠላሙን በማስጠበቅ በኩል ያለው ድርሻ ወደር የለውም።

ኢትዮጵያ በተለይ በአሁኑ ወቅት ከየትኛውም ህዝብና መንግሥት ጋር ተስማምቶ የመኖር፣ ሰጥቶ የመቀበል የውጭ ፖሊሲ ያላት ሀገር ነች፡፡ ያም ሆኖ ሀገራችን በጀመረችው ፈጣን ለውጥና የህዳሴ ጉዞ ምክንያት ዕንቅልፍ የሚያጡ ጠላቶች በዙሪያዋ ተፈጥረውባታል። ከዚህ አንጻር እንደ ኤርትራ መንግሥትና አልሻባብን የመሳሰሉ ፀረ ሠላምና የጥፋት ኃይሎችን ተደገጋሚ አካሄድ አብነት አድርጎ መጥቀስ ይቻላል፡፡

በሰላሙ መንገዳችን በአብሮ እንልማ መርሀችንም እንደ አለመታደል ሆኖ ጠላት ብናፈራም፤ የጠላት ቅስምንና አከርካሪን መስበር የሚያውቀበት መከላከያ ሰራዊት ስላለን ደግሞ ከእድልም በላይ እድለኞች ሆነናል።

የጠላቶቻችን እኩይ ተግባርና የጥፋት መንገድ በጀግናው የመከላከያ ኃይላችንና በምልዐተ ህዝቡ ብርቱ ጥረት ከአንዴም ሁለት ሦስት ጊዜ እንዲመክን ሆኗል፡፡ ከ15 ዓመታት በፊት በተሳሳተ ስሌት ሀገራችንን የወረረው ሻእቢያ ዳግም ይፋዊ ጦርነት በማይለኩስበት ደረጃ ተኮላሽቶ ተቀምጧል፡፡ አልሻባብም ጎረቤት ሶማልያን ስርዓት አልባ በማድረግ ጅሃድ አውጆ ሀገራችንን ለማጥቃት ቢዝትም ምኞቱን እዛው ከበቀለበት ምድር ፈቅ ሳይል ማምከን ተችሏል፡፡ የሶማልያ ህዝብም እፎይታን አግኝቶ በአዲስ የምርጫ ስርዓት መሪውን እስከመምረጥ ያደረሰው በመከላከያ ኃይላችን ግንባር ቀደም አስተዋጽኦ ነው፡፡ ይሄ ለጀግና ህዝብና ሰራዊት ትልቅ ኩራት ነው።

ትናንት  በኢትዮጵያ ሳማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ለ5ኛ ጊዜ በተከበረው የመከላከያ ቀን ላይ እንደተገለፀውም፤ ዘመን የማይሽረው የኢትዮጵያዊያን ጀግንነትና አርበኝነት አሁንም በመከላከያ ኃይላችን እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ለዚህም ነው የዕለቱ መሪ ቃል “በህዝባዊ መሠረት ላይ የተገነባው ጀግንነታችን እየታደሰ ይኖራል” የሚል ጠንካራ ሀሳብን ያነገበው፡፡

በስነስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመም ጀግናው የመካላከያ ኃይላችን የህዝብና መንግሥት አደራን ተቀብሎ እየፈፀመ ላለው ተግባር አመስግነዋል፡፡ ይህን ዘመን የማይሽረው ጀግንነት ተጠቅሞና፣ ህዝባዊነቱን ጠብቆ ለወደፊቱም ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎችን እየመከተ የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል እንዲተጋም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣን፣ የመከላከያ ባለከፍተኛ ማዕረግ አዛዦች፣ የጅግጅጋ ከተማ ህዝብና የደቡብ ምስራቅ ዕዝ አባላት በተገኙበት በዚህ ደማቅ ስነስርዓት ላይ የተከናወነ አንድ ታሪካዊ ተግባርም ነበር፡፡ ይኸውም የኢትዮጵያዊያን የጀግንነትና አርበኝነት ውርስ እንደ ወራጅ ወንዝ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚፈስ መሆኑን ያስመሰከረ ገድል ነው፡፡

ይህ በወርቃማ የታሪክ መዝገብ ተከትቦ ወደ ሌላ ትውልድ የሚሸጋገረው ጀግንነትም፤ የደቡብ ምስራቅ ዕዝ የ13ኛው ክፍለ ጦር 4ኛ ሬጅመንት አዛዦችና አባላት በሶማልያ በሃልሜን አውደ ውጊያ ውሎ የፈጸሙት ጀግንነት ነው።

አልሻባብ ለዓመታት የደረሰበትን ተከታታይ ጥቃት ተከትሎ ባለ በሌለ ኃይሉና በውጭ ሀገሮች ድጋፍ ጭምር ታግዞ ሰኔ 2 ቀን 2008 ዓ.ም በጀግኖቹ ኢትዮጵያዊያን ምሽግ ላይ ይዘምታል፡፡ ጨለማን ተገን አድርጎ፤ በከባድ መሳሪያ ታግዞ በመከላከያ ኃይላችን ካምፕ ላይ የከፈተውን ውጊያ በጀግንነት በመመከት በመልሶ ማጥቃት ታሪክ የማይረሳውን የአርበኝነት ተግባር የፈፀመችው ይህች 4ኛ ሬጅመንት ነበረች፡፡ የሬጅመንቱ አባላትም ላስመዘገቡት ከፍተኛ ድልና  ጀግንነት 2 ደረጃ የሚዳሊያ ሽልማት ከፕሬዚዳንቱ እጅ ተቀብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ፊት ኩራትና ክብርንም ተቀዳጅተዋል፡፡

በአውደ ውጊያው የተሰው የሬጅመንቱ አዛዥ ኮሎኔል ጌጡ ዳምጤና ሌሎች ሰማዕታትም በክብር ተወስተዋል፡፡ መቼም ለማይነጥፈው ኢትዮጵያዊ ጀግንነት ዳግም ምስክር ሆነዋል፡፡ በዚህ አርዓያነት ኢትዮጵያዊያን ሁላችን ለሀገራችንና ለህዝቦቿ ሰላምና ብልፅግና አርበኞች መሆን ይኖርብናል፡፡ ታሪክ ሰሪዎችም ልንሆን ይገባል፡፡   

Published in ርዕሰ አንቀፅ

የህወሓት (የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ) 42ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የፊታችን ቅዳሜ የካቲት 11 ቀን 2009 ዓ.ም ይከበራል። ይህ ቀን የድርጅቱ ታጋዮች  የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከጭቆና አገዛዝ ነፃ እንዲወጡ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት ነው። የትግራይ ህዝበ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በመሆን ለ17 ዓመታት ባደረገው መራር ትግል፤ በከፈለው የህይወት፣ የአካልና የደም መስዋዕትነት አገሪቱ ከአስከፊው የደርግ አገዛዝ ነፃ ወጥታ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድና በአንድነት የመሠረቷትን አዲሲቷን ኢትዮጵያ መገንባት ጀምረዋል።

ዛሬም ድረስ በህይወት ያሉ ታጋዮች በ17 ዓመቱ ትግል ዓላማቸው መሳካቱ ሁሌም ደስታ ቢሰጣቸውም፤ በትግሉ ወቅት ልጆቻቸውን በሞት ያጡ ቤተሰቦች እና የተለያየ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ታጋዮች ግን «ምንም እንኳ የታገልነው ለኢትዮጵያ ህዝቦች ነፃነትና ፍትህ መስፈን ቢሆንም ዛሬ ላይ ተርስተናል»ይላሉ።

ታጋይ አስመላሽ ግደይ፤ በ1972 ዓ.ም ትግሉን እንደተቀላቀሉ፤ እስከ ትግሉ ማብቂያ መታገላቸውንና በደረሰባቸው ጉዳትም እስከአሁን ድረስ ከፍተኛ የሆነ የጤና ችግር እንዳለባቸው ይናገራሉ። «ለህዝብ ታግለን ውጤት በመምጣቱ ልዩ ደስታ ይሰማኛል። ሆኖም በ17 ዓመቱ ትግል ልጆቻቸውን  ያጡ ወላጆች ጧሪና ተንከባካቢ የላቸውም። እንደ እኔ አካል ጉዳተኛ ሆነው የሚሰቃዩና ዛሬ አስተዋሽ ያጡ ታጋዮችም አሉ።  በትግሉ አካልችን የጎደለ ታጋዮችና ልጃቸውን ያጡ  ወላጆች ጭምር በከፈልነው መስዋዕትነት ልክ ተጠቃሚ አልሆንም» በማለት ቅሬታቸውን ያቀርባሉ።

ታጋይ አስመላሽ «በትግሉ ወቅት አንተ ከምትሰዋ እኔ ቀድሜ ልሰዋ እንዳልተባባልን ዛሬ ተጋዮች ተረሳስተናል፤ መረዳዳትና መተባበራችን ከድል በኋላም ቀርቷል። ለአገርና ለህዝብ መስዋዕት የከፈለ ታጋይ ከድል በኋላ ተረስቶ መንገድ ላይ መውደቁ ያሳዝናል። ልጆቻችን የአገርና የህዝብ ፍቅር እንዲኖራቸው ከፈለግን ለአገር ሲሉ መስዋዕት የሚከፍሉ ሰዎችን ማክበርና መደገፍ  ይገባናል» ብለዋል።

ታጋይ ወለደሩፋዔል ሀይላይ በበኩላቸው፤ «በትግሉ ወቅት ከሞት በላይ የሚያስከፍል መስዋዕትነት ቢኖር እንኳ አንዱ ለአንዱ ታጋይ ለመክፈል ዝግጁ ነበርን። በጦርነት ወቅት ቆስሎ ስቃዩን በጩኸት ማሰማት እና ወደ ኋላ መሸሽ እንደነውር ይቆጠር ነበር። ዋናው ዓላማችን  የህግ የበላይነትና ዴሞክራሲ የሰፋነባት አገር መፍጠር ነበር። በህይወት ቆይተን በበርሀ የሰነቅነው ራዕይ ተሳከቶ ማየታችን ልዩ ሀሴት ፈጥሮልናል» ይላሉ።

እርሳቸው እንዳሉትም፤ የታገሉለት ዓላማ ለኢትዮጵያ ህዝብ የመናገር፣ የመጻፍና ሌሎች በርካታ መብቶችን አጎናጽፏል። በትግል ወቅት «ትልቁ ፈተና ከድል በኋላ ነው» ይባል ነበር። በትግሉ ወቅት  የአካል ጉዳት የደረሰባቸውና ልጆቻቸውን ያጡ ወላጆች ዛሬ በችግር ውስጥ ናቸው። ለምሳሌ በየካ ክፍለ ከተማ በጦርነቱ ዓይናቸው የጠፋ፣ እግራቸው የተቆረጠና የተለያዩ አካል ጉዳት የደረሰባቸው 20 ታጋዮች በረንዳ ላይ ወድቀዋል። ህወሓት የወደቁትን ታጋዮች መሰብሰብ አለበት።

ታጋይ የማነ ንጉሰ፤ በሰሓርቲ ሳምረ ወረዳ በ1973 ዓ.ም ወደ ትግል የተቀላቀለ ሲሆን፤ በ1985 ዓ.ም ወለጋ ላይ ከኦነግ ጋር በተደረገው ውጊያ የህብለ ሰረሰር የአካል ጉዳት ደርሶበታል። ታጋዩ የታገለለት ዓላማ ግቡን ስለመታ ደስታው ወደር እንደሌለው ይገልጻል። ነገር ግን አንድም ቀን ስለግል ኑሮው ባያስብም አገሪቱ ስታድግ የታጋዩ ህይወትም አብሮ ይለወጣል የሚል እምነት ነበረው። ነገር ግን ይሄ በአብዛኛው አልሆነም። በትግሉ ወቅት ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ታጋዮች በዘበኝነት፣ በልመና እና  እነርሱን በማይመጥን ሥራ ተሰማርተው ማየቱ እንደሚያሳዝነው ተናግሯል።

ታጋይ አባዴ ገብረሥላሴ ትግሉን ሲያስታውሱ ፤ «እንደ እሬት መራራ እንደ ማርም ጣፋጭ ነበር» ይላሉ። እርሳቸው እንደሚሉት ትግሉን መራራ የሚያደርገው ብዙ ጓዶች ለህዝብና ለብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነፃነት መሰዋታቸው ነው። ጣፋጭ የሚያደርግው ደግሞ በዚያ መራራ ትግል ውስጥ እኔ ቀድሜ ልሙት እንጂ ቀድመህ ሙት የሚል አንድም ታጋይ አለመኖሩ ነው። 

ከትግል በኋላም ታጋዮችም ሆኑ የኢትየጵያ ህዝቦች በተለያየ ደረጃ ተጠቃሚ ሆነዋል። ደረጃውም የሚወሰነው በመልፋትና ባለመልፋት መካከል ነው። ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆነው በለፋው ልክ ነው። በዚህም የተነሳ በማህበራዊውም ሆነ በኢኮኖሚ ልዩነቶች ይኖራሉ። በታጋዮችም  ሆነ በሌላው ህብረተሰብ መካከል የመደጋገፍ ችግር ይኖራል። ችግሩ እንዲፈታ ሁሉም ከሠራ ግድፈቶች እየተስተካከሉ ይመጣሉ ብለዋል።

የትግራይ የጦር ጉዳተኞች ማህበር የቦርድ አባል አቶ ዓለም ገብረመስቀል፤ «ተረስተናል» የሚለው የተጋዮቹ ቅሬታ ትክክል እንዳልሆነ ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት «ቅድመ ነገር የተከፈለው መስዋዕትነት በገንዘብ የሚለካ አይደለም። መስዋዕትነቱ የተከፈለው ለህገ መንግሥታዊ ስርዓት ነው»ሲሉ ያነሳሉ።

አቶ ዓለም እንደሚሉት፤ የተከፈለው መስዋዕትነት በገንዘብ የሚለካ ባይሆንም በትግል ወቅት የተለያየ ጉዳት የደረሰባቸው ታጋዮች  አልተረሱም። ማህበሩ በትግሉ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸውን ታጋዮች ተጠቃሚ ለማድረግ 25ሺ አባላትን አቅፎ ተመስርቷል። በአራት ደረጃ መድቦ እንደየጉዳያቸው መጠን ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛል።  በአዲስ አበባና በክልል እስከ ቀበሌ ድረስ መዋቅር በመዘርጋት ለተወሰኑት ቤት ሠርቶ ሰጥቷል። በየወሩም ድጎማ ያደርጋል። ሌሎቹም በአቅማቸው ቤት እንዲሠሩም ያለማስያዣ በዝቅተኛ ወለድ ብድር ተመቻችቶላቸዋል። ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩም ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው። የሚደረገው ድጋፍም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለና ያለባቸውን ችግር በመገምገም በተለይም ለሴቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተሠራ ነው።

በሚደረገው ድጋፍና በአካል ጉዳተኞቹ ጥረት ታጋዮቹ በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ ናቸው። ከራሳቸው አልፎም አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች በመሳተፍ በየዓመቱ ተሸላሚና ሞዴሎች መሆናቸውን አቶ ዓለም አረጋግጠዋል።

 

ዜና ሐተታ

አጎናፍር ገዛኽኝ     

Published in የሀገር ውስጥ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንኮች ከወለድ ነጻ በሆነው የአገልግሎት አይነት ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰባቸውን ገለጹ።

የሁለቱ ባንኮች የስራ ሀላፊዎች ለአዲስ ዘመን ብቻ በሰጡት መረጃ እንደገለጹት፤ ከእምነታቸው ጋር በተያያዘ የባንክ ወለድ የማይበሉና የማይከፍሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በተጀመረው ከወለድ ነጻ አገልግሎት በሶስት ዓመት ውስጥ ብቻ አራት ቢሊዮን ብር ሊሰበስቡ ችለዋል።

የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እንደሚሉት፤ ባንኩ እአአ በ2013 ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥም 136 ሺ ደንበኞችን አፍርቷል። ከእነዚህ ደንበኞቹም አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ችሏል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻም፤ ባንኩ ከ850 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብም ደንበኞች የሚፈልጉትን ዕቃ ገዝቶ ሰጥቷል። በአሁኑ ወቅትም በ211 ቅርንጫፎች አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል። በቀጣይም አገልገሎቱን ለማስፋፋትና ኢኮኖሚውን ይበልጥ ለማገዝ እየሰራ ነው።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሙኒኬሽን ክፍል ተጠባባቂ ስራ አስኪያጅ አቶ በልሁ ታከለ እንደገለጹት፤ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ስራ የጀመረው እኤአ በ2013 ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ ባንኩ በመላ አገሪቱ ባሉ 730 ቅርንጫፎቹ  ከ375 ሺ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች የተሟላ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

እንደ አቶ በልሁ ገለጻም፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በኋላ ሶስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ችሏል። ይህ ከፍተኛ ገንዘብ በመሆኑ አገልግሎቱን በቀጣይ ይበልጥ ተደራሽ ማድረግ ከተቻለ ከዚህም በላይ ገንዘብ መሰብሰብና ኢኮኖሚውን ይበልጥ ማገዝ የሚቻልበት እድል አለ።

ባንኮቹ ከመደበኛው ተቀማጭ ሂሳብ በተጨማሪ ከወለድ ነጻ አገልግሎቱ የየባንካቸውን የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር ለሚሰሩት ስራም አገልግሎቱ የራሱን አስተዋፅኦ እያበረከተላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

 

ጌትነት ምህረቴ

Published in የሀገር ውስጥ

 

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የአግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም  በማሳደግ፤ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች እንዲቋቋሙ በመደገፍ፣ የመጠጥ ኢንዱስትሪዎች አቅም አጠቃቀምን 90 በመቶ በማድረስ ለውጭ ገበያ ከቀረቡ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ምርቶች 300 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ግብ ተጥሎ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ እቅድ ሳይሳካ አምስት ዓመቱ ተጠናቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች በኢኮኖሚው ውስጥ ያላቸው ድርሻ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ ከ10በመቶ አይበልጥም፡፡ ይሄንን መጠን በዓቅዱ መጨረሻ ዘመን ወደ 25 በመቶ ከፍ በማድረግ አምስት ቢልዮን ዶላር ገቢ ለማመንጨት ታቅዶል፡፡ በ2017 ዓ.ም ደግሞ ድርሻውን ወደ 40 በመቶ ለማድረስ ዕቅድ ተቀምጧል፡፡

ይህንኑ እቅድ ለማሳካት በአማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች አራት የተቀናጁ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡ በአራቱ ክልሎች በጠቅላላው ሊለማ የታቀደው የእያንዳንዱ ፓርክ ስፋት አንድ ሺህ ሄክታር መሬት ሲሆን፤ ከዚህ ውሰጥ በሙከራ ደረጃ በቅድሚያ የሚለማው 250 ሄክታር መሬት እንደሆነ ታውቋል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት አካል የሆነውና በጎጃም ቡሬ የሚገነባው ፓርክ የመሰረት ድንጋይ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን ተቀምጧል፡፡

የእነዚህ አራት ፓርኮች ግንባታ ተጠናቆ በሙሉ አቅም ወደስራ ሲገቡ በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን 82 ሺህ ቶን መጠን ያላቸው የተለያዩ የግብርና ምርቶች ይመረታል፤ ከሽያጫቸውም 52 ቢሊዮን ብር ገቢ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታው ዶክተር መብራቱ መለስ እንደሚናገሩት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት በሁሉም ክልሎች 17 የግብርና ቀጣናዎች የተለዩ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ አራቱ ፓርኮች በሚቀጥሉት ዓመታት በፍጥነት ግንባታቸው ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ይገባሉ፡፡

የፓርኮቹ መገንባት አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ የተያዘው ዕቅድ አካል መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ድኤታው፤ በፓርኮቹ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች በተደራጁት ኢንስቲትዩቶች አማካይነት ውጤታማ የማኔጅመንት፣ የቴክኖሎጂና የአሠራር ማሻሻያ ድጋፎች ከዚህ ቀደም ከነበረውም በላይ እደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ የብድር አቅርቦትንም በማሻሻል የኢንዱስትሪ ልማቱን የማፋጠን ሥራ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

አቶ ክቡር ገና የፓን አፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር እና የኢኒሼቲቭ አፍሪካ መስራች ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ በኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ በፓርኮች መገንባት፣ የሰው ኃይል በማሰልጠንና መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ላይ እንደ ሀገር መሰረታዊ መግባባት አለ፡፡ ጥያቄው እንዴት ወደሥራ መግባት አለበት የሚለው ነው? የመጀመሪያው ተግባርም ህዝብ የመንግሥት አቅጣጫን ማበረታታት፤ ለተሰሩ ሥራዎች አውቅና መስጠት መሆን አለበት፡፡

«ጥሬ እቃዎችን ሀገር ውስጥ በማምረት እሴት በመጨመር የውጭ ግብዓትን ሳይጠቀሙ ኤክስፖርት በማድረግ የአካባቢው ገበሬ ተሳታፊ ሆኖ ጥሬ እቃውን በትክክል እዲያቀርብ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡  ሰፋፊ እርሻዎች ከሀገራችን አቅም አንፃር በጥናት ሲታይ ከሚወስዱት ግብዓት እና የአስተዳደር ወጪ አንጻር ውጤታማ አይደሉም፡፡ ስለሆነም የፓርኮች መገንባት ወደ ኢንዱስትሪ መግባት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ጊዜያቸውን ሳያጠፉ ቀጥታ ወደሥራ እንዲገቡ ያስችላል፡፡ ስለሆነም እየተኬደበት ያለው መንገድ አዋጭና ተመራጭ ነው»  አቶ ክቡር፡፡

ዶክተር ሀሰን ቡሽራ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ናቸው፡፡ እርሳቸውም በፓርኮች ልማት ላይ ያላቸው አቋም ከአቶ ክቡር ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ፓርኮቹ አርሶዓደሮች የተሻሉ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙና ትስስር እንዲፈጥርላቸው በማድረግ ብቁ እና ተወዳዳሪ ምርቶችን ማምረት መቻል አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት ከወዲሁ ድጋፍ ሊያደርግና አስቦበት መግባት አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከፓርኮቹ ስፋት አንፃር ከቦታው ለሚነሱ ዜጎች ተገቢውን ካሳ ከመፈፀም አልፎ በሚቋቋሙ ኢንዱስትሪዎች የሀብት ተጋሪነት እዲኖራቸው በማድረግ ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅትና በታዓማኒነት መስራት እንደሚያስፈልግ ዶክተር ሀሰን ያሳስባሉ፡፡ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እጥረት እዳያጋጥም ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎቹ ሲቋቋሙ የሚያመርቱት ምርት፣ የሚጠቀሙት ግብዓትና የሚሸጥበት ቦታ ከወዲሁ መታሰብ አለበትም ብለዋል፡፡

«የመንግሥት ሚና ፓርኮቹን መገንባት ብቻ ሳይሆን ወቅታዊ አስተማማኝ መረጃዎችን ማቅረብ ፤ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት መካከል የተቀናጀ አሰራር እንዲኖር ማድረግ፤ ምርቱን ለማስፋፋትና አምራቾች የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል፤ አስተማማኝ የብድር አገልግሎት ማቅረብ፤ በአመራረትና በማቀነባበር የእሴት ሰንሰለት ደረጃዎች በቂ እና አስተማማኝ የስልጠና አቅርቦት እንዲኖር ማድረግና በዝቅተኛ ዋጋ የሚገኙ ተስማሚ የማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂ ግብአቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ለዘርፉ ዕድገት የራሱን አስተዋፆ ማድረግ አለበት» ነው ያሉት ዶክተር ሀሰን፡፡

እንደ ዶክተር ሀሰን ማብራሪያም፡ የግል ባለሀብቱ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ገብቶ ከመሳተፍ አልፎ የምርምር ተቋማትን በመክፈት የዘርፉን ግንባታ በማገዝ ምርቶች በሚፈለገው መጠን፣ የጥራት ደረጃና ዓይነት እዲመረት ማገዝ መቻል አለበት፡፡ የግብይት ትስስርና የምርት ቅብብል ሂደት ቀልጣፋ እና ተወዳዳሪ እንዲሆንም ባለሀብቶች በትብብርና በቅንጅት መስራት አለባቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች እና የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆችም ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሙያ ክህሎትና ብቃት ያለው የሰው ሀይል ማፍራት መቻል አለባቸው፡፡

 

ዜና ሐተታ

አየናቸው እሸቱ

Published in የሀገር ውስጥ
Wednesday, 15 February 2017 18:55

መርካቶና ግብር ውሃና ዘይት

በኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ጭምር ትልቁ የገበያ ቦታ እንደሆነ የሚነገርለት መርካቶ፤ በውስጡ 22 ሺ መንግሥት የሚያውቃቸው ህጋዊ ነጋዴዎች መኖራቸውን የገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን መረጃ ያሳያል። ከበላስልጣኑ የመርካቶ ቁጥር 1 እና 2 ግብር መሰብሰቢያ ቅርንጫፎች በ2008 ዓ.ም አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን  ብር ግብር ተሰብስቧል። ይሁን እንጂ  የመርካቶ ነጋዴዎች የህግ ተገዥነት 25 በመቶ ብቻ እንደሆነ በ2004 ዓ.ም የተካሄደው የባለስልጣኑ ጥናት ያመለክታል።

ይህ ማለትም ከተጠቀሰው የነጋዴዎች ቁጥር (22 ሺህ) 75 በመቶ የሚሆነው፤ ግብሩን አያሳውቅም፣ ግብር ይሰውራል፣ በወቅቱ አይከፍልም፣ ደረሰኝ አይቆርጥም፣ ህጋዊ ያልሆነ ደረሰኝ አትሞ ይሰጣልና ሌሎች ሌሎች ህገ ወጥ ተግባራትን ይፈጽማል የሚል አንድምታ እንዳለው  በባለስልጣኑ የአዲስ አበባ ታክስ ፕሮግራም ልማትና ስራዎች ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር  ወይዘሮ ነፃነት አበራ ይናገራሉ።

አዲስ ዘመን በመርካቶ ተዘዋውሮ ለመመልከት ባደረገው ጥረት፤ “በቫት ወይስ ያለ ቫት” ይሁንልህ በሚል ሽያጭ የሚፈጽሙ ነጋዴዎች ብዛትና ድፍረት ከፍተኛ መሆኑን አረጋግጧል። ሀሳባቸውን ለጋዜጣው ሪፖርተር የሰጡ ነጋዴዎችም፤ መንግሥት ከህዝብ የሚሰበሰበውን የተጨማሪ እሴት ታክስ ነጋዴዎች ለእራሳቸው ሲያውሉ ዝም ብሎ ተመልክቷል፤ በኮንትሮባንድና በጥቁር ገበያ ህጋዊ ነጋዴው አደጋ ተጋርጦበት እየወሰደ ያለው እርምጃ አጥጋቢ አልሆነም፤ የገቢ ሰብሳቢ ተቋማቱ ሰራተኞች ከሁሉም ነጋዴ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ታክሱን ከመሰብሰብ ይልቅ ኪራይ ሲሰበስቡ ይታያሉ፤ በአጠቃላይም የንግዱን ዘርፍ እንደፈለጉ የሚያሾሩ ከመንግሥትም በላይ አቅም ያላቸው ትላልቅ የግለሰብ ነጋዴዎች ተፈጥረዋል ሲሉ ገልጸዋል፤ ወቅሰዋል።

የባለስልጣኑ የታክስ ፕሮግራም ልማትና ስራዎች ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ነፃነት፤ የተጠቀሱት ችገሮች መኖራቸውን ያምናሉ። የችግሮቹ መንስኤም ኮንትሮባንድና ጥቁር ገበያ መሆኑን ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉትም በግብር አሰባሰቡ ላይ ትልቅ ደንቃራ እየሆኑ ያሉት አስመጪዎች ናቸው። «አስመጭዎቹ ለሚያስገቡት እቃ ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆነውን ዶላር የሚያገኙት ከጥቁር ገበያ ነው። በዚህም አብዛኛው ግብይት የባንክ ስርዓትን ተከትሎ የሚሄድ አልሆነም። ከጥቁር ገበያ ባገኙት ዶላርና በኮንትሮባንድ ወደ አገሪቱ ውስጥ ያስገቡትን እቃ ያለደረሰኝ መሸጥ ስለሚቸገሩ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል በተለይም በመርካቶ በስፋት ህገ ወጥ ደረሰኝ አትመው እቃውን እየሸጡ ናቸው» ሲሉ የችግሩን ስፋት አብራርተዋል።

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻም፤ ህገ ወጥ ተግባሩ በባለስልጣኑ የስለላ የስራ ክፍል ተጠንቶ ተረጋግጧል፤ ብዙዎቹ ህገ ወጦችም እየታወቁና እየታሰሩ ናቸው። ህገ ወጥ የደረሰኝ ህትመት በስፋት እያካሄዱ ያሉትም ትላልቆቹ ነጋዴዎች መሆናቸው ተደርሶበታል። ህገወጥ ስራውን ከሰሩ በኋላ ተጠያቂ እንዳይሆኑ የንግድ ፍቃዳቸውን በሊስትሮዎች፣ ገጠር በሚኖሩ ሰዎችና  በቤት ሰራተኞቻቸው ስም እንደሚያወጡ ታውቋል። ህገ ወጥ ተግባሩን ለማስቆምም በአዲስ አበባና ይሁን በአገር ደረጃ ቅንጅት ተፈጥሮ እየተሰራ ነው።

የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል ዋና ዳይሬከተር አቶ ገመቹ ወዮማ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ ጥቁር ገባያን አስመልከቶ ያደረገው ጥናት መኖሩን ይጠቅሱና፤ በጥቁር ገበያ የሚገኘው ዶላር ለኮንትሮባንድ እቃ መግዣ እንደሚውል መረጋገጡን ተናግረዋል። ኮንትሮባንድና ጥቁር ገበያን ለመከላከልም በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አማካኝነት የተለያዩ አካላት የተካተቱበት ኮሚቴ መቋቋሙን ጠቁመውም፤ ኮሚቴው ወደ ስራ ሲገባ ችግሮች እንደሚቃለሉ አቶ ገመቹ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የህግ አማካሪ የሆኑት አቶ ዮሴፍ ገብሬ፤ እስካሁን ኮንትሮባንድና ጥቁር ገበያን ለማስቀረት በሚያስችል ደረጃ የተቀናጀ ስራ እንደሌለ ነው የሚናገሩት። ችግሩን ለመቅረፍም የዓለም አገራትን ተሞክሮ በመቀመር ህገ ወጥ ኮንትሮባንድና ጥቁር ገበያን የሚከላከሉ የድንበር ጠባቂዎችና የፋይናንስ ፖሊስ ማቋቋም እንደሚበጅ መክረዋል።  

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ስራ ትምህርት ቤት የአካውንቲንግና የንግድ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ሀላፊና መምህር አቶ ታረቀ አያሌው፤ ታክስ በአግባቡና በተገቢ ሁኔታ ተሰብስቦ ለሚፈለገው ዓለማ ካልዋለ የሀብት መመጣጠንና የስራ ዕድል ፈጠራ አይኖርም። የዋጋ አለመረጋጋትና ሌሎች ችግሮችም ይፈጠራሉ ይላሉ።

መምህሩ እንደሚገልጹትም፤ በኢትዮጵያ ግብርን በአግባቡ የመሰብስብ ችግር አለ። ሸማቹ በነጋዴው አማካኝነት ለሚሰበሰበው እንደ ተጨማሪ እሴት አይነት ታክሶችም ደረሰኝ በመጠየቅ የዜግነት ግዴታውን አይወጣም። ነጋዴውም ታክሱን ከህዝብ ሰብስቦ በተገቢው ሁኔታ በመስጠት ችግር አለበት። ግብር አስከፋዩም ተከታትሎ የመቆጣጠር ከፍተኛ የሆነ ክፍተት ይታይበታል። በዚህም ሁሉም ነጋዴ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ግብር ስለማይከፍሉ አንዳንድ ነጋዴዎች ከበርቴዎች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ እየቆረቆዙ ናቸው። 

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በታክስ ላይ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን እየሰሩ ያሉት አቶ ለሜሳ ባይሳ፤ በኢትዮጵያ ዝቅተኛ ግብር ለመሰብሰቡ ምክንያቱ በግብር ዙሪያ በመንግሥትና በህዝብ መካከል መተማመን አለመፈጠሩ፣ ፍትሃዊ የግብር አወሳሰን አለመኖር፣ ተመሳጥረው ግብር በሚያስቀሩ ባለሃብቶች ላይ መንግሥት ተገቢና አስተማሪ ቅጣት አለመውሰዱ ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን በጥናት ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

አቶ ለሜሳ እንደተናገሩት፤ ዜጎች ግብር ከፋይ እንዲሆኑ የአገር ፍቅርን መገንባት የግድ ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ በተለያየ ደረጃ ያሉ መሪዎች የእራሳቸውን ጥቅም ወደ ጎን በመተው አገራዊ ሀላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው። ይህ ተግባር የአገር መውደድ ስሜትን በዜጎች ላይ ስለሚፈጥር ሀቀኛ ግብር ከፋይ መፍጠር ይቻላል። ነጋዴዎችም የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት አለባቸው። ግብር ሰብሳቢውም ከጥቅም መረብ የጸዳና ሁሉንም በእኩልና በታማኝነት የሚያገለግል መሆን አለበት። ይህ ከሆነ የተሻለች አገር መገንባት ይቻላል።

የንግድ ስራ ትምህርት ቤት መምህሩ አቶ ታረቀ በበኩላቸው፤ ግብር ሰብሳቢው የማስፈጸም አቅሙን ማሳደግና ከዘመቻ  ስራ መውጣት አለበት ሲሉ ይመክራሉ። የሂሳብ ባለሙያዎች ማህበራትን በማጠናከር የሥነ ምግባር ደንብ እንዲኖርና በዚያ መሰረት እንዲሰሩ ማድረግ ያስፈልጋል። የሚወጡት ህጎች ሁሉም ነጋዴዎች ላይ እኩል ተግባራዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ የግድ ይላል። ትላልቅ ነጋዴዎች ለትናንሾቹ ሲሸጡ ለማን እንደሸጡ መረጃ እንዲይዙ በማድረግ ናሙና በመውሰድ በደረሰኝ መሸጥ አለመሸጣቸውን ማረጋገጥ ይገባል። መንገድ ላይና አየር በአየር የሚሸጡ ነጋዴዎችም ግብር እንዲከፍሉ ማድረግ ለፍትሀዊነት ሲባል የግድ ነው ብለዋል።

ጥቁር ገበያና ኮንትሮባንድ ግብር በአግባቡ እንዳይሰባሰብ እያደረጉ ስለሆነ፤ በአደባባይ በሚካሄዱት እነዚህ ተግባራት ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰድ አለበት። የጥቁር ገበያን ከምንጩ ለማድረቅም ባንኮች የተለያዩ አሰራሮችን በመዘርጋት መስራት አለባቸው። ኮንትሮባንድ ለማስቀረት ደግሞ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግና ተቆጣጣሪው አካልም እራሱን መፈተሽ አለበት። ከዚህም በተጨማሪ ነጋዴዎች ከባንክ የሚሰጣቸውን የመግዣ ዶላርና የገባውን እቃ በማመሳከር ከተሰጠው እቃ በላይ ካስገቡ እርምጃ መውሰድ ቢቻል ለውጥ ማምጣት ይቻላል ሲሉ ባለሙያዎቹ መክረዋል።  

 

ዜና ትንታኔ

አጎናፍር ገዛኽኝ 

 

Published in የሀገር ውስጥ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።