Items filtered by date: Thursday, 16 February 2017

ምክር ቤቶች  በህዝብ ውክልና የሚቋቋሙ የመንግሥት ከፍተኛው አካል ናቸው። በዚህ ረገድ ፌዴራላዊ ሥርዓት በምትከተለው ኢትዮጵያም የክልል መንግሥታት የራሳቸውን ምክር ቤት በማቋቋም የተሰጣቸውን ተልዕኮ እየተወጡ ይገኛሉ። ለዛሬ ከአማራ ክልል ምክር ቤት  አፈ ጉባዔ አቶ ይርሳው ታምሬ ጋር  በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቃለ መጠይቅ ይዘን ቀርበናል።

አዲስ ዘመን ፦  የአማራ ክልል ምክር ቤት የክልሉን ህዝቦች በመወከል ረገድ በአካባቢ፣ በፆታ፣ በዕድሜና በማህበረሰብ ክፍል ስብጥሩ ምን ይመስላል?

አቶ ይርሳው ፦ ምክር ቤቱ የሕዝብን ቀጥተኛ ውክልና ለማረጋገጥ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ይዟል፡፡ የአርሶ አደሩ ውክልና ሰፋ ያለ ነው፡፡ የሴቶች ውክልና ከጠቅላላው የምክር ቤቱ አባላት 47 በመቶ ነው፡፡ የንግዱን ማህበረሰብ፣ምሁራንና ወጣቶችንም ታሳቢ አድርጓል፡፡ ስለዚህ ከሞላ ጎደል ከሁሉም የኀብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ ነው፡፡ በተዋረድም የሚገኙት ምክር ቤቶች በተመሳሳይ ሁኔታ የተለያየ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ናቸው።

አዲስ ዘመን ፦ የኀብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ ለተፈፃሚነታቸው የምታደርጉት ክትትል ምን ይመስላል?

አቶ ይርሳው ፦  ምክር ቤቱ ሦስት ተልዕኮዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው የአካባቢን ልማት፣ ዴሞክራሲ፣  ሰላምና ማህበራዊ ፍትህ ለማምጣት የሚያስችል ሕግ ማውጣት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ነው፡፡ ይሄም የአስፈጻሚና የዳኝነት አካሉን ዕቅድ እንዲሁም አፈጻጸም ይመረምራል፡፡ ከዚያ በመነሳት ውሳኔዎችን ያስተላልፋል፡፡ ሦስተኛ ውክልናን መወጣት ነው፡፡ አባላቱ የሕዝቡ ቀጥተኛ ወኪል ስለሆኑ የሕዝቡን ችግርና ፍላጎት በሚገባ ተረድተው እንዲፈታ የሚያደርጉበት መስተጋብር አለ፡፡

ምክር ቤቱ ስድስት የቋሚ ኮሚቴ አደረጃጀቶች አሉት፡፡ በእርግጥ የክልል ምክር ቤት እንደ ፌዴራሉ ምክር ቤት አባላቱ በቋሚነት አይቀመጡም፡፡ ነገር ግን የቋሚ ኮሚቴ ስብሳቢዎች በቋሚነት ቢሮዎችን ይከታተላሉ፤ የሕዝብ ቅሬታዎችን ያዳምጣሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ጉባዔ ለማካሄድ በሚቃረቡበት ወቅት ሁሉም የቋሚ ኮሚቴ አባላት የመስክ ቅኝት ያደርጋሉ፡፡ ሪፖርት ይመረምራሉ፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ ጉባዔ እናካሂዳለን፡፡ ለዚህ ጉባዔ የክልሉ መንግሥት የስድስት ወር አፈፃፀም ምን ይመስል ነበር? የሚለውን ወረዳና ቀበሌ ድረስ ወርደው አይተው ለመመለስ ስምሪት ላይ ናቸው፡፡ እንደተመለሱ የእያንዳንዱን ተቋም ሪፖርት ይገመግማሉ፤ ሪፖርቱንና መስክ ላይ ያዩትን ወስደው የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ ያቀርባሉ፡፡ ምክር ቤቱ ያን ይዞ ይወያያል፤ ይወስናል፡፡

አዲስ ዘመን ፦  አባላቱ በመስክ ቅኝት የሚመለከቷቸው የአፈጻጸም ክፍተቶችን ተከታትሎ ውሳኔዎች እንዲወሰኑ ግፊት ይደረጋል?

አቶ ይርሳው፦  አዎ! ይሄን ሁሉም የአገሪቱ ዜጋ መታዘብ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ውይይቱ የሚደረገው በክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀጥታ ስርጭት ነው፡፡ ምክር ቤታችን የአንድ ፓርቲ አባላት ያሉበት ምክር ቤት አይመስልም፡፡ በማንኛቸውም ጉዳዮች ላይ በግልጽ ይወያያል፤ ይከራከራል፤ ከዚያም ባለፈ በልዩነት ጭምር ይወስናል፡፡ በጣም በርካታ ውሳኔዎችን በድምፅ ብልጫ ወስኗል፡፡

አዲስ ዘመን ፦  በማሳያነት ማንሳት የሚቻሉ የልዩነት ውሳኔዎች አሉ?

አቶ ይርሳው ፦ ሹመት ላይ በልዩነት ይወስናል፡፡ በሚቀርቡ ሪፖርቶች ዙሪያ በማፅደቅና ባለማፅደቅ ዙሪያ፤ በአዋጅ እንዲሁም ብዙ ውሳኔዎች በልዩነት ተወስነው ያውቃሉ፡፡ ኀብረተሰቡ ውስጥ በአብዛኛው በአንድ ፓርቲ ምክር ቤት ውስጥ በልዩነት ይወስናል የሚል ግምት የለም፤ በእኛ ምክር ቤትም ይህ አመለካከት እንዳይኖር እየተሰራ ነው፡፡ ምክንያቱም የሕዝብ ጥቅም የምናስከብረው በዚህ መንገድ ስንሰራ ብቻ ነው በሚል እንወያያለን፡፡

በተጨማሪም አባላቱ ከተለያየ የኀብረተሰብ ክፍል የተውጣጣ መሆኑም ምክር ቤቱን ጠንካራ አድርጎታል፡፡ ለምሳሌ አርሶ አደሮችና ሴቶች የጎላ ድርሻ አላቸው፤ ያዩትን ነገር በቀጥታ ትክክለኛውን ችግር በማቅረብ ይጋፈጡታል፡፡ ውይይቶቹ ችግሮችን ያሳያሉ፤ ምክር ቤቱም እንዲታረሙ ውሳኔ ያሳልፋል፡፡ ምክር ቤቱ ‹‹ችግር አለ›› ብሎ ከወሰነ በኋላ ችግሩ ሳይፈታ ሲቀር፤ ውሳኔ ከማሳለፍና ከመከራከር ባለፈ እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ከዚህ አንጻር የሚቃረን ነገር አለ ብለን ገምግመናል፡፡ 

አዲስ ዘመን ፦  ምክር ቤቱ በክትትል ደረጃ በበቂ ሁኔታ እንዳልሄደ የገመገማቸው ጉዳዮች የሉም?

አቶ ይርሳው፡- በርካታ የሕዝብ ጥያቄዎች አሉ፡፡ እነኛ ሁሉ ተፈተዋል ማለት አይቻልም፡፡ በግምገማ ውጤት መሰረት ጥያቄዎችን ባነሳነው ልክ ተፈፃሚ ሳይሆን ሲቀር ያልፈጸመውን አካል እርምጃ መውሰድ አለመቻል ነው፡፡ አሁን ያልተፈጸሙ ጉዳዮችን እየለቀሙ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ማቅረብ ጀምረዋል፡፡ ነግር ግን እርምጃ ማስውሰድ ላይ የሚቀረን ሥራ አለ፡፡ ለዚህ አንዱ ምክንያት የአስፈጻሚው አካል የብቃት ችግር ነው፡፡ ሕዝቡ የሚያነሳው ጥያቄ በጣም ብዙ ነው፡፡ በምትሄድበት መንደር በሙሉ የአስፋልት ጥያቄ ያነሳል፡፡ ነገር ግን እንደ መንግሥት የተነሱትን ጥቄዎች በሙሉ መመለስ አይቻልም፡፡ ስለዚህ የሚፈቱት ላይ አተኩሮ መነጋገር ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ፦  ከሌሎች ክልሎች ምክር ቤቶች ጋር ሲነጻጸር በጥንካሬ የሚጠቀሱ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

አቶ ይርሳው ፦  በየስድስት ወሩ ተገናኝተን ሥራ የምንገመግምበትና ልምድ የምንለዋወጥበት የሁሉም ምክር ቤቶች መድረክ አለን፡፡ በዚህ ረገድ ከሌሎች ክልሎች የምናገኛቸው ልምዶች አሉ፡፡ ከእኛ ክልልም የሚወሰድ ልምድ በሚል በጋራ እውቅና ከተሰጣቸው አንዱ ምክር ቤቱ የግልፅነትና ተጠያቂነት ሥርዓት ሊያሰፍን የሚችል የቀጥታ ስርጭት ውይይት ማካሄዱ ይጠቀሳል፡፡ ምክር ቤቱ የሚያደርገው ትግል በሌሎች ክልሎች በጥንካሬው ይበረታታል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ዓመት አዲስ መንግሥት ሲቋቋም ከፍተኛ የሆነ ውይይት ነበር፡፡

አዲስ ዘመን ፦  በኀብረተሰቡ በኩል የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በግልጽ ለይቶ መፍትሄ ከመጠቆም አንጻር ክፍተት የለም ?

አቶ ይርሳው ፦  ምክር ቤቶች የሚነጋገሩት የሕዝቡን ጥያቄ ይዘው ነው፡፡ ጥያቄውንም በተለያዩ መንገዶች ያገኙታል፡፡ አባላቱ የሚኖሩት ከሕዝቡ ጋር ነው፡፡ ስለዚህ ኀብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ችግር ይዘው ይመጣሉ፡፡ በሌላ በኩል በዋናው ምክር ቤት የሚገኙ የክልሉ ወኪሎችና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት በዓመት አንድ ጊዜ በተደራጀ ሁኔታ ወደ መራጩ ሕዝብ ሄደው ያወያያሉ፡፡ በውይይት የሚነሱት ችግሮች በወረዳ፣ በዞን፣ በክልልና በፌዴራል ደረጃ የሚፈቱ ይሆናሉ።

አባላቱ መፍትሄዎቹን በተመለከተ ለወረዳና ለዞን የቤት ሥራ ሰጥተው ይመጣሉ፡፡ ወደ ክልል የሚመጣው ደግሞ በሪፖርት ተደራጅተው ርዕሰ መስተዳድሩና የካቢኒ አባላት ባሉበት ችግሮችን ይለያሉ፡፡ ወደ ፌዴራል የሚመጣውንም የፌዴራል ፓርላማ አባላት ይዘው ይመጣሉ፡፡ ሦስተኛው በቋሚ ኮሚቴ በኩል ሲወርዱ የተሰራውን ሥራና ሕዝቡን በአካል አግኝተው ያነጋግራሉ፡፡ በእነዚህ መንገዶች የተገኙትን ችግሮች ነው አባላቱ ጉባዔ ላይ የሚነጋገሩት፡፡ ማጠንጠኛቸውም የሕዝቡ ትክክለኛ ጥያቄ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦  በአምስተኛው ዙር የክልሉ ምክር ቤት ምን ውሳኔዎችን አሳልፏል?

አቶ ይርሳው፦   ጎላ ብሎ የሚነሳው ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የቅማንት የማንነት ጥያቄ ዙሪያ ምክር ቤቱ ሁለት ጊዜ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ አንደኛው ውሳኔ የቅማንት ብሔረሰብ የራሱ ማንነት ያለው ብሔረሰብ ነው የሚል ውሳኔ ወስኗል፡፡ በተጨባጭ በጥናትም 42 ቀበሌዎች ላይ የሚኖር የቅማንት ሕዝብ አለ፡፡ ይሄን ይዘን ተግባራዊ መደረግ አለበት በሚል ወስኗል፡፡ ይሄ ውሳኔ የምክር ቤቱ ውሳኔ በመሆኑ አስፈፃሚው ሊመልሰው የማይችል ውሳኔ ነው፡፡

ባለፈው ዓመት ሌላ ክርክር ተነስቶ ስለነበር እርሱን መሰረት ተደርጎ ከ42ቱ ቀበሌዎች ውጪ ሌሎች ‹‹ቅማንት ነን›› የሚሉ የኀብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄ አላቸው፡፡ ነገር ግን የሚኖሩት ተቀላቅለው ነው፡፡ ይሄን በተመለከተ ምክር ቤቱ በስፋት ተወያይቶ አማራና ቅማንት ተቀላቅለው የሚኖሩባቸውና ከ42ቱ ቀበሌዎች ጋር ኩታ ገጠም የሆኑ ቀበሌዎች በሕዝበ ውሳኔ እንዲለይ የሚለውን አስፈጻሚው እንዲወስን ምክር ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ አሁን ይሄ እየተሰራ ነው ያለው፡፡ ሕዝብ እየተወያየ ነው፤ አሁን በሕዝበ ውሳኔ እንጨርሰው ወደሚል ስምምነት እየተደረሰ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦  ባለፈው ዓመት በክልሉ ተከስቶ የነበረውን የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ለመፍታት የምክር ቤቱ ሚና ምን ነበር?

አቶ ይርሳው፦  ባለፈው ዓመት በክልላችን የተፈጠረው ችግር በጠቅላላ ምን ይመስላል? የሚል ራሱን የቻለ ሪፖርት ባለፈው የምክር ቤታችን ጉባዔ  እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ ችግሩ እንዴት ተፈጠረ? ለምን ተፈጠረ? እንዴት ተፈታ? ወደፊት እንዳይደገም ምን መደረግ አለበት? በሚል ርዕሰ መስተዳድሩ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ሰፊ ውይይት ተደርጎ ምክር ቤቱ በሦስት ጉዳዮች ውሳኔ አሳልፏል፡፡

አንዱ ውሳኔ ምክር ቤቱ ከቅማንት ጋር የተያያዘውን ጉዳይ በፈታበት መልኩ ውሳኔ ባሳለፈበት መንገድ ይፈጸም የሚል ነው፡፡ ሁለተኛ ከትግራይ ክልል ጋር ያለው የድንበር ጥያቄ ሁለቱ ክልሎች በጋራ ተቀምጠው ይፍቱ፡፡ ይህ ካልሆነ ጥያቄው ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትሎ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሄዳል የሚል ውሳኔ ወስኗል፡፡

ሦስተኛው የወልቃይት ጉዳይ ነው፡፡ የወልቃይት ጉዳይ ትግራይ ውስጥ የሚገኙ አማራ ነን የሚሉ ሕዝቦች ጥያቄ ነው፡፡ በሕገመንግሥታችን ደግሞ አንድ ክልል ውስጥ እየኖረ የማንነት ጥያቄ አለኝ የሚል የኀብረተሰብ ክፍል ጥያቄውን እንዲያቀርብ የሚፈቀደው ለሚኖርበት ክልል ነው፡፡ ስለዚህ የወልቃይት ጥያቄ ለአማራ ክልል ምክር ቤት ሊቀርብ የሚገባው ጥያቄ አይደለም፡፡ ጥያቄ አለን የሚሉ አካላት ጥያቄያቸውን በሚኖሩበት ክልል ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትለው ሊያቀርቡ ይገባል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የእኛ ምክር ቤት አጀንዳ አድርጎ ውሳኔ ሊያሳልፍ የሚችልበት ነገር ሊኖር አይገባም በሚል ወስኗል፡፡

አዲስ ዘመን፦ ጉዳዩ ሁለቱን ክልሎች የሚመለከት እንደመሆኑ በጋራ እያከናወናችሁ ያላችሁት ነገር አለ?

አቶ ይርሳው፦  በምክር ቤት ደረጃ ሁለቱ ክልሎች የተለየ እንቅስቃሴ አላደረጉም፡፡ ነገር ግን የሁሉም ክልሎች የጋራ ፎረም አለን፡፡ በዚያ መንገድ እንነጋገራለን፡፡ የተለየ ነገር ግን የለም፡፡

አዲስ ዘመን፦  በሰሜን ጎንደርና በምዕራብ ትግራይ መካከል በወሰን ጉዳይ የተነሳ የሚታየውን አለመግባባት ለመፍታት የተጀመረው ሥራ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?

አቶ ይርሳው፡- ይሄ የምክር ቤቱም ጥያቄ ነው፡፡ ምክር ቤቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ተወያይቶ ይሄ ጥያቄ በሁለቱ አስፈጻሚ አካላት እልባት ማግኘት አለበት በሚል ወስኗል፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ መጀመሪያ የመንግሥት መዋቅር በሚገባ መጠናከር አለበት፤ ጥያቄውን በአግባቡ ለመፍታት የመንግሥት አካላት በራሳቸው ችግር ውስጥ ነበሩ፡፡ ስለዚህ በሁለቱም አካላት በኩል መንግሥት በተሃድሶ አስተሳሰባቸውን በማነፅና መልሶ በማደራጀት መጀመሪያ መዋቅሩን እናጠናክር፡፡ ከዚያም እርሱን ይዘን እንሰራለን የሚል  ነበር፡፡ ምክር ቤቱ በቀጣይ ጉባዔ ሲያካሂድ ይሄን ጉዳይ መልሶ ‹‹ወስነን ነበር፤ የት ደረሰ?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ እንደ አንድ አመራር ያለውን ሁኔታ የማውቀው በዚህ ደረጃ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦  ጥያቄው ወዳልተፈለገ አጀንዳ እንዳይቀየር ከማድረግ አንጻር የተከናወኑ የግንዛቤ ሥራዎች አሉ?

አቶ ይርሳው፦  በእኛ በኩል ምን መስራት አለብን? የሚለውን ተመልክተናል፡፡ ‹‹ጥያቄ አለን›› የሚሉ የኀብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ የማንነት ጥያቄም ይሁን ከዚያ የዘለለ ሊሆን ይችላል የሚነሱ የኀብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ ይሄን ማንሳት ሕገመንግሥታዊ መብት ነው፡፡ በየትኛውም ክልል ተመሳሳይ ነገር ይነሳል፡፡ ጥያቄውን ማንሳት የሚችሉት ግን ሕጉ በሚፈቅደው መልኩ መሆን አለበት፡፡ በክልሉ ምክር ቤት የሚያረካ ውሳኔ ካልተሰጠ አቤቱታውን ይዘው ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መምጣት ይችላሉ፡፡

እንደ ክልላችን መሰራት ያለባቸው ነገሮች ግን አሉ፡፡ በአንድ በኩል የኀብረተሰብ ክፍሎቹን ጥያቄ ምክንያት በማድረግ የብጥብጥ ማዕከል የሆነው እኛ ነን፡፡ እየተጎዳን ያለነው እኛ ነን፡፡ እየሞቱ ያሉት የእኛ ዜጎች  ናቸው፡፡ ስለዚህ ትክክለኛውን ጥያቄ ትክክለኛ ካልሆነው ጋር መለየት እንዲችል ኀብረተሰቡ ላይ ሰፊ ሥራ ማከናወን አለብን፡፡ ምክንያቱም ጎንደር አካባቢ አማራ ተበደለ እያሉ ጉዳዩን ከፍ አድርጎ የማስጮህ ነገር አለ፡፡ ይሄን በአስተሳሰብ ግልፅ ማድረግ ያስፈልጋል ተብሎ በተለይ በሰሜን ጎንደር አካባቢ የአመራር መልሶ ማደራጀቱ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ የክልል አመራር ድጋፉም ከሌሎች ዞኖች በተለየ እንዲደረግ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ኀብረተሰቡ ጉዳዩን በትክክለኛው ሚዛን እንዲያየው ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ግልፅ ማድረግ ይገባል በሚል የጋራ ስምምነት እየተሰራ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦  የተጠቀሰውን የግንዛቤ ችግር ለመፍታት የተሄደው ርቀት በቂ ነው?

አቶ ይርሳው፦  በቂ ነው ብለን አናምንም፡፡ ምክር ቤቱ ያስቀመጠውም የበለጠ መስራት አለብን በሚል ነው፡፡ እንዲያውም በዚህ ጉዳይ ላይ ግልፅ ውይይት ሲደረግ ጎልቶ የታየው የግንዛቤ ችግሩ ነው፡፡ አንደኛ አንዳንዶች ትግራይ ውስጥ ያለው የወልቃይት አማራን ጥያቄ የአማራ ክልል መንግሥት እንደሚፈታው ያስባሉ፡፡ ‹‹ለምን አትፈቱም?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹አማራ ተበደለ፤ ጥያቄ ያነሳ ሰው ታሰረ›› የሚለው ኀብረተሰብ ውስጥ በሰፊው ሰርጿል፡፡ ሦስተኛ አብረው የሚኖሩ ምናልባትም የተለየ ጥብቅ ትስስር ባላቸው ሕዝቦች መካከል ተገቢ ያልሆነ ቁርሾ ተፈጥሯል፡፡ ይሄን ቁርሾ መፍታት አለብን፡፡ ይሄን ለመፍታት ምክር ቤቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ እየተሰራ ነው፤ ነገር ግን ከዚህ በላይ መስራት ይቀረናል፡፡

አዲስ ዘመን፦  ለጉዳዩ ከሚሰጥ አተረጓጎም ጋር በተያያዘ በምክር ቤቱ አባላት በኩልስ የሚታይ ክፍተት አልነበረም?

አቶ ይርሳው፦  አባላቱ የኀብረተሰቡ ወኪሎች በመሆናቸው ይሄ ችግር በምክር ቤቱ ሊጠፋ አይችልም፡፡ ከሕዝቡ ውስጥ ነው የወጡት፡፡ ሕዝቡ ውስጥ የአመለካከት ልዩነት አለ፡፡ ይሄ ልዩነት ከሕዝቡ በተቀዳ ምክር ቤትም ይኖራል፡፡ በውይይት ጊዜ በግልፅ የተለያዩ አቋሞች ይሰማሉ፡፡ እንደ ምክር ቤት ግን መናገር ያለብን ምን ሃሳብ ተነሳ? ሳይሆን የተነሱት ሃሳቦች በምን ተጠቃለሉ? በምን ተደመደሙ? የሚለው ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦  በክልሉ አንዳንድ ዞኖች ፍትሃዊ የልማት ስርጭት አለመኖሩ ይነሳል፤ ይሄን ምክር ቤቱ እንዴት ያየዋል?

አቶ ይርሳው፦  ትክክል ነው፡፡ በተለይ ባለፉት 15 ዓመታት የመንግሥት አፈጻጸም ላይ ውይይት ሲደረግ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችግር በተለያየ ቦታ መኖሩን መገንዘብ ተችሏል፡፡ ምከር ቤቱ የደመደመው ነገር በተለይ የክልሉ ከፍተኛ ቆላማ እና ከፍተኛ ደጋማ አካባቢዎችን የልማት ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ መሰረታዊ ችግር እንዳለ ነው፡፡ የኑሮ ደረጃውም በዚህ መልኩ የሚገለጽ ነው፡፡ የሰሜን ጎንደር ቆላማ አካባቢዎች፣ የዋግህምራ ቆላማ አካባቢዎችና ሌሎችም ተመሳሳይ አየር ንብረት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ የኀብረተሰቡ ተጠቃሚነት በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ በከፍተኛ ደጋማ አካባቢዎች የሚገኘው የኀብረተሰብ ክፍልም አሁንም በከፋ ድህነት ውስጥ ይገኛል፡፡ ስለዚህ በክልሉ ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ላይ  ችግር  ነበር  የሚል ግምገማ   ተደርጓል ፡፡

ምክር ቤቱ መሰረተ ልማት በተለይም መንገድን በተመለከተ በዚህ ዓመት አይደለም የገመገመው፡፡ በ2008 ዓ.ም በግልፅ ተወያይቶ ሰሜን ጎንደር አካባቢ የሚገኝ የመንገድ ትስስር መሰረታዊ ችግር አለበት ብሎ ለይቷል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ይሄን ችግር መፍታት አለበት የሚል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ አስፈጻሚውም ይሄን ይዞ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመነጋገር በዚህ ዕቅድ ዘመን አብዛኛው የአስፋልት ሽፋናችን ሰሜን ሸዋና ሰሜን ጎንደር ላይ ነው፡፡ የገጠር መንገድም አብዛኛው ሰሜን ጎንደር እንዲሸፍኑ ተደርጎ እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ ስድስት የልማት ኮሪደሮች በተፋሰስ ተለይተው ቢቀመጡም ያለውን አቅም ያህል እያለማን አይደለም በሚል ተገምግሟል፡፡ በመሆኑም ውጤታማ ማድረግ ቀጣዩ ሥራ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦  ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ ኀብረተሰቡን ከሚያማርሩ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳል፤ በፕሮጀክቶች ቁጥጥር ላይ ያላችሁ ቁርጠኝነት ምን ያህል ነው?

አቶ ይርሳው ፦  በክልሉ የፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ በጣም መሰረታዊ ችግር አለ፡፡ በ2007 ዓ.ም አንድ ጥናት ተደርጎ ፕሮጀክቶች ከተያዘላቸው የኮንትራት ጊዜ በላይ መውሰዳቸው አንድ ችግር ሆኖ ተለይቷል፡፡ ሁለተኛው ችግር በተቀመጠው የጥራት ደረጃ አለመሰራት ነው፡፡ ሦስተኛው ከአቅም በላይ የፕሮጀክቶች መለዋወጥ ነው፡፡ በዚህ ላይ ብቻ ሳይሆን የንብረትና ግዢ አስተዳደራችንም ችግር እንዳለበት ታይቷል፡፡ ስለዚህ በምክር ቤቱ በኩልም ዋና የትኩረት ነጥብ ሆኗል፡፡ በዚህ መልኩ እንሄዳለን አንሄድም የሚለውን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን ፦  ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎችን ምክር ቤቱ እንዴት ይገመግመዋል ?

አቶ ይርሳው ፦ ምክር ቤቱ ይሄን ጉዳይ የዕለት ከዕለት አጀንዳው አድርጎ አያነሳም፡፡ ነገር ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች ጉዳዮች ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ የተለያዩ አካባቢዎች የክልሉን ተወላጆች ቅር የሚያሰኙ ድርጊቶች ተፈፅመውባቸው ነበር፡፡ ይሄን መነሻ አድርጎ ምክር ቤቱ ተመካክሯል፡፡ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ የክልሉን ተወላጆች መንግሥት መጠበቅ አለበት በሚል ውይይት ተደርጓል፡፡ መጨረሻ ላይ የተደረሰው ስምምነት እንደ መንግሥት ከሌሎች አካባቢ ከሚኖሩ አማራዎች ጋር ግንኙነት መፍጠር ያስፈልጋል የሚል ነው፡፡

ነገር ግን በመሰረታዊነት ሌላ ክልል ላይ የሚኖር አማራ መብት የሚከበረው በአማራ ክልል አይደለም፡፡ በመሰረታዊነት መብታቸው የሚከበረው በሚኖሩበት አካባቢ በሚኖር ሚዛናዊ አስተዳደር ነው፡፡ ስለዚህ እንደ አገር ሚዛናዊ አስተዳደር እንዲኖር ትግል ማድረግ አለብን፡፡ በታሪክ አጋጣሚ የአማራ ክልል ተወላጅ የሌለበት ክልል የለም፡፡ ስለዚህ በዚህ ሁሉ ክልል ተወካይ ልኮ ማስተዳደር አይቻልም፡፡ በመሆኑም የተጠቀሰው አስተሳሰብ እንዲኖር የራሳችንን ሚና መወጣት አለብን የሚል ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

አዲስ ዘመን፦  ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ይኖራል?

አቶ ይርሳው፦  እንደ አገርም እንደ ክልልም የተነሱ ችግሮች ነበሩ፡፡ አሁንም ሕዝባችን የሚፈልገው የተቆጠረ ሥራ ነው፡፡ የተነሳው ችግር ተፈትቶ ማየት ይፈልጋል፡፡ ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆን ሪፖርት መስማት ይፈልጋል፡፡ ሌላው መስራት የማንችል ከሆነ መስራት ለምን እንደማንችል በግልፅ ማሳየት አለብን፡፡ ከዚህ ውጪ የሆነውን ነገር ሕዝቡ አይቀበልም፡፡ በተደጋጋሚ ሕዝቡ የሚለን ‹‹ችግር ታዳምጣላችሁ ግን አትፈቱም›› ነው የሚለን፡፡

ሁሉም የመንግሥት አካላት ችግሮችን ፈትተው ለሕዝቡ ማሳያት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለያየ ምክንያት መፍታት የማይቻል ከሆነ ደግሞ በአሳማኝ ምክንያት ማስረዳት ይጠይቃል፡፡ ሕዝባችን ችግርን የመግለፅ ክፍተት የለበትም፡፡ ስለዚህ መፍትሄ የሚሰጥና የሚያገለግል መንግሥት መፈጠር አለበት፡፡ እኛም መስራት ያለብን የመንግሥት አካላት እውነትም ለሕዝቡ አገልጋይ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ሕዝቡም የልማት ጥያቄ ሲያቀርብ አቅምን ባገናዘበ መልኩ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡      

አዲስ ዘመን ፦ ለትብብርዎ  በጣም እናመሰግናለን !

አቶ ይርሳው፦  እኔም አመሰግናለሁ !

ብሩክ በርሄ

Published in ፖለቲካ

ጉዳዬን ሳሰላስል መተረት አማረኝ፡፡ .… አንድ ሰነፍ ተማሪ ነው አሉ፡፡ ሰርክ እንደተበላሸ ተሸከርካሪ የአስኳላን ደጃፍ የሚረግጠው ተገፍቶ ነው፡፡ ከወላጆቹም ቢሆን የዘወትር አተካራው ጥናት አለመውደዱና ትምህርት ቤት መጥላቱ ነበር፡፡ ብቻ እንደነገሩ የደንብ ልብሱን አጥልቆ ከቤት ውልቅ ይላል፡፡ ከወላጅ የከረረ ቁጣ ለማምለጥ ሲል ይሄን ዘወትር ሳይወድ ያደርገዋል፡፡ እንደምንም ክፍል ገብቶ ቢቀመጥም እንደ ብርቱ አቻዎቹ ቀልቡን ለመምህሩ አሳልፎ ከመቸር ይልቅ፤ ክፍለ ጊዜው ቶሎ አልቆለት ወደሚናፍቀው ስንፍና መቼ እንደሚመለስ ጠልቆ ያሰላስላል፡፡

ከእለታት አንድ ቀን ስንፍናውን በሚገባ የታዘቡ የሒሳብ መምህር፤ በድኑን ሰይሞ በሀሳብ ከሸፈተበት ዓለም ለመመለስ ቀላል ጥያቄ ያቀብሉታል፡፡ ልጁ ግን ስለመቀነስ የሒሳብ ስሌት ያስተማሩት ምንም ስላልገባው በጥያቄው ይደናገጣል፡፡ ብልሁ መምህር ግን ተስፋ በመቁረጥ ‹‹አንተን ከማጎበዝ ዶክተር ማደደብ ይሻላል›› አላሉትም፡፡ ይልቁኑም ጥያቄውን ይበልጥ ለማቅለል በማሰብ የእውቀት ማገዶ ፈጂውን ተማሪ በምሳሌ ማስረዳት ገፉበት፡፡

‹‹እሺ፤ በረት ውስጥ አምስት በጎች አሉህ››፤ ‹‹በጀ›› ተማሪው ቀጣዩን ይጠብቃል፡፡ ‹‹ከአምስቱ በጎች አንዱ ሾልኮ ቢያመልጥ ስንት ይቀሩሃል?›› ሲሉ ይጠይቁታል፡፡ ተማሪውም ቀበል አድርጎ ‹‹ኸረ መምህር ምንም አይቀረኝ›› ይላል፡፡ በምላሹ ብግን ያሉት መምህር ‹‹ይህ እንዴት አይገባህም?›› ብለው ቢጮሁ፤ ተማሪው እያለቀሰ ‹‹ኸረ መምህር የበጎችን አመል ጠንቅቄ ነው የማውቀው፤ አንዲቷ ካመለጠች ሌሎቹም ተከትለዋት ነው የሚጠፉት›› በማለት ስህተቱን አሽሞንሙኖ በብልጠት ለማምለጥ ሞከረ፡፡ መምህሩም በምላሹ ከመሳቅ ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡

ምን ያድርጉ? ‹‹ማሽላ እያረረች ትስቃለች!›› ይባል አይደል፡፡ በነገራችን ላይ በየመስኩ የሰነፉን ተማሪ ባሕሪ የተላበሱ አይጠፉም፡፡ በትምህርትም ባይሆን የታዘዙትን ስራ በአግባቡ ላለማከናወናቸው ማምለጫ እንዲሆን ከስሌት ያፈነገጠ አመክንዮ እየደረደሩ ዙሪያ ጥምጥም የሚሄዱ ብዙ ናቸው፡፡ መቼም የሒሳብ ቀመር ላይ የፍልስፍና ነፋስ ሽው ካላለ በቀር የአንድ ሲደመር አንድ ውጤቱ ሁሌም ከሁለት ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን ለስንፍናቸው መከለያ ይሄን ስሌት የሚያዛቡ አይጠፉም፡፡

በመንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የታዘዙትን ስራ ወይም የተቋሙን ዓመታዊ ዕቅድ አቅርበው፤ ‹‹ምነው ይሄ አፈጻጸም ዝቅተኛ ሆነ?›› ሲባሉ፤ ለድክመቱ አሳማኝ ምክንያት ማስቀመጥ ይሳናቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ድክመትን በመቀበል ነገ ለመታረም ከመዘጋጀት ይልቅ ‹‹የበጎችን ባህሪ ጠንቅቄ አውቀዋለው›› የሚል አይነት ማምለጫ ይጠቀማሉ፡፡ ነገር ግን በየትኛውም የስራ አፈጻጸም ውስጥ በትጋት የተሞላ ብቃትና ቁርጠኝነት ካለ ‹‹አንዱን አስወጥቶ ሌሎቹን በጎች ለማስቀረት›› ብልሃት አይጠፋም፡፡

ወደ ነጥባችን እንመለስ፡፡ ኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት  አንስቶ አሁን እስከምንገኝበት ዓመት መግቢያ ድረስ በዘለቀ የሰላም ችግር ማለፏ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተነሳው የሰላም መደፍረስ ያስከፈለው አገራዊ ዋጋ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በኢኮኖሚው በርካታ የአገር ውስጥና የውጪ ኢንቨስትመንቶችን ጨምሮ በቱሪዝም፣ በግብርና እንዲሁም በንግድና ሌሎች ምጣኔ ሀብቶች አፈጻጸም ላይ አሉታዊ አሻራውን አትሟል፡፡ በረጅም ጊዜ የአገሪቱ  ዕቅዶችም ላይ የተወሰነ መጓተትን ፈጥሯል፡፡ በአጠቃላይ የሰላም አይተመኔ ዋጋ በሰላሙ መናጋት ወቅት በሚገባ ተንፀባርቋል፡፡ 

ለዚያም ነው፤ መንግስት የችግሮቹን ጥልቀት በሚገባ መዝኖ መንግስታዊ ግዴታውን በተለያየ መልኩ በመወጣት ተግባር ተጠምዶ የከረመው፡፡ ከምንም በላይ ለዘላቂ ልማት ዋልታና ማገር የሆነውን የሰላም አየር ለመመለስ ብዙ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ችግሩን ‹‹የሌሎች ጥፋት›› በሚል ቸልታ ከማለፍ ይልቅ፤ ጥንስሱን ከመሰረቱ መለየት በሚያስችል ደረጃ ‹‹ውስጤን እመለከትበታለሁ›› በማለት መንግስታዊ መዋቅሩን በጥልቅ የተሃድሶ ወይራ ሲያጥን ሰንብቷል፡፡

ከመንግስት ሹማምንት ቀጥሎ ወደ ፈጻሚው የወረደው የተሃድሶ መድረክ በሲቪል ሰርቫንቱ በተለይም በፈጻሚው ውስጥ ያለውን የአመለካከት ክፍተት ለማመላከት እንዳስቻለው አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን የተሿሚዎቹን የስራ ብቃት ፈትሾ የአመራር ለውጥ የማድረጉን ያህል ለአፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን ‹‹የሰላም መደፍረስ ያመጣው ነው›› በሚል ‹‹ሽፋን›› ላለፈ የውስጥ ድክምቶቻቸው መጋረጃ የሚያደርጉትን መለየት ይገባዋል፡፡ በእርግጥ የሰላም መደፍረሱ ያመጣውን ችግር በፍፁም መካድ አይቻልም፡፡ ሆኖም ችግሩን ከዕቅድ ትግበራ ወቅትና ስፍራ ጋር ሳያገናዝቡ ደጋግሞ በምክንያትነት እየጠቀሱ ከተጠያቂነት ለማምለጥ መዳዳት አዋጭ አይሆንም፡፡          

ሰሞኑን በስራ አጋጣሚ በተገኘሁባቸው ጥቂት የማይባሉ የዕቅድ ግምገማ መድረኮች ‹‹የፀጥታ ችግር›› የሚለው ምክንያት በዝቶ ታዝቤያለሁ፡፡ እንደሚታወቀው የምንገኝበት ወር የዓመቱ ስራ አፈጻጸም በየዘርፉ የመንፈቅ ተሞክሮ የሚፈተሽበት ነው፡፡ በተገኘሁባቸው የተቋማት የስድስት ወራት ዕቅድ አተገባበር ፍተሻ ወቅት ለተለያዩ ንዑስ ዘርፎች ዝቅተኛ መሆን የጠቀስኩት ምክንያት ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡

ምክንያት መኖሩ ባልከፋ፡፡ ነገር ግን ከታማኝነት ያፈነገጡ ዙሪያ ጥምጥም ምክንያቶችን መደርደር የዛሬን ስንፍና ለመቀበል ፈቃደኛ ካለመሆን ባሻገር በቀጣይም ለመሻሻል የፍላጎት ዋስትና ይነፍጋል፡፡ ይሄ ደግሞ ከማስተዛዘብ አልፎ የሚያስጠይቅ ድክመት ይሆናል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ አንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን ጠርቶ ‹‹በስድስት ወሩ ምን አቅደህ፤ ምን ተገበርክ?›› ሲል ይጠይቃል፡፡ መስሪያ ቤቱ ለአገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ግኝት የአንበሳውን ድርሻ የሚወጣ ግዙፍ ዘርፍን ይመራል፡፡ ይሄ ዘርፍ በጥቂት መዘናጋት ብዙ አገራዊ ጥቅም የሚታጣበት፤ ይበልጥ በተጉ ቁጥር ደግሞ ብዙ ጥቅም የሚያሳፍስ ወሳኝ መስክ ነው፡፡

እንደራሴዎቹ ብቻ ሳይሆኑ መንግስትና ሕዝብ ከአፈጻጸሙ ብዙ የሚጠብቁበት በመሆኑ ግምገማቸው ብርቱ ነበር፡፡ ሆኖም የተቋሙ ሪፖርት በአብዛኛው እንደሚያመላክተው በስድስት ወራት ውስጥ ብዙ አቅዶ ያሳካው አነስተኛ መሆኑን ነው፡፡ የግምገማ ደንብ ነውና በጉዳዩ ላይ ምላሽና ማብራሪያ ለመስጠት ከሚኒስቴሩ ከፍተኛ ሃላፊዎች እስከ መካከለኛ አመራሮች በስፍራው ታድመዋል፡፡ ለተነሱት ጥቄዎችም ‹‹መልስ›› ያሉትን ዘረዘሩ፡፡ የሚያስገርመው ነገር በስራ ሃላፊዎቹ ሲጠቀስ እንደሰማሁት ከእያንዳንዱ ደካማ አፈጻጸም ጀርባ ‹‹የፀጥታ ችግር›› የሚለው ተደጋግሞ በምክንያትነት መሰማቱ ነው፡፡

የገዛ ትዝብቴ የእንደራሴዎቹም ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ እያንዳን ዳቸውን ምላሾች እያነሱ ‹‹የሰላም መደፍረስ የነበረባቸው ስፍራዎች ውስን ናቸው፤ በተጨማሪም የሰላም መደፍረሱ ጊዜና የዕቅዱ መፈጸሚያ ወቅት የተናበቡ አይደሉም›› በሚል ከሁሉም ድክመቶች ጀርባ መነሳቱ እንዳላስደሰታቸው ጠቀሱ፡፡ ሃላፊዎቹ ግን ‹‹የበጎችን አመል ጠንቅቄ አውቀዋለሁ›› በሚል አይነት አቋማቸው ገፉ፡፡ እደግመዋለሁ፤ በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሁኔታው አሳማኝ ቢሆን እንኳን አመለካከቱ በተመሳሳይ መልኩ ከገፋ የቀጣዩ ስድስት ወራት ክንውንም ስጋት ውስጥ ይወድቃል፡፡

ከጠቀስኩት ተቋም በተጨማሪ ‹‹ከፀጥታ ችግሩ ጋር በቀጥታ የመገናኘት እድላቸው አነስተኛ ነው›› ተብሎ በሚገመቱትም ሳይቀር ምክንያቱ መደጋገሙ ስጋቴ ከንቱ እንዳይሆን አደረገው፡፡ አሁን አገሪቱ ወደተረጋጋ መስመር እየገባች ነው፡፡ በመሆኑም ቀጣዮቹ ጊዜዎች ካለፈው ስድስት ወር በእጥፍ ትጋትን የሚጠይቁ መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም፡፡ በሰላም መደፍረስ የባከኑትን ወርቃማ የልማት ጊዜያት ማካካስ ያስፈልጋል፡፡ የአገሪቱ ቁልፍ የልማት ጥያቄዎች የሚመለሱበት መንገድ ‹‹ከናዳው በፈጠነ›› ቅልጥፍና መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

እናም እኔ ይሄን እላለሁ፤ ከምንም በላይ የሰላም ጥቅም መተኪያ የለውም፡፡ ስለዚህ ሰላም ለማንም ተብሎ የሚተው ተራ ጉዳይ አይሆንም፡፡ ነገር ግን ድክመታችንን ተከትሎ ለሚሰነዘር ሂስ የማያባሩ ሰበብ አስባቦችን ደጋግሞ መደርደር እምነት ይሸረሽርብናል፡፡ ሰላም ለልማት እንደሚስፈልግ ሁሉ ሰላምም የአገር ልማትን አጥብቆ ይሻል፡፡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥቄዎችም መልስ የሚያገኙት በቁርጠኝነት ማገልገል ሲቻል ነው፡፡ ያኔ ሰላም ለልማት፤ ልማቱም በሰላም ተደጋግፈው ይዘልቃሉ፡፡ እስከመቼ? ድህነት እስኪረታ! እስከየት? እስከ ብልፅግና መዳረሻ!

ሚሊዮን  ሺበሺ

Published in አጀንዳ

የቀረጥ ነጻ ዕድል ልማትን የማበረታቻ አንዱ ስልት ነው። መንግስት ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለተሰማሩ ባለሀብቶችና አምራች ድርጅቶች የቀረጥ ነጻ  ፈቅዷል።  የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መረጃ እንደሚያመለክተው በ2000 ዓ.ም  በሀገሪቱ 9 ቢሊዮን  ብር የነበረው የቀረጥ ነጻ እድል በ2008 ዓ.ም ወደ 71 ቢሊዮን ብር አድጓል።

መረጃው የቀረጥ ነጻ  እድሉን የመጠቀም አዝማሚያው በከፍተኛ ደረጃ ማሻቀቡን ያመለክታል። ይህ በአገሪቱ  ከአለው እድገት ጋር ተያይዞ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በቱሪዝምና በሌሎች ዘርፎች ከውጭ የሚገቡ ግብአቶች ፍላጎት ስለመጨመሩ ማሳያ ነው። በህግና ስርዓቱ መሰረት ከተመራ ብቻም  የቀረጥ ነጻ እድሉን ያጣጣሙት የየዘርፎቹ ተዋንያን  ትሩፋቱን የመቋደስ ተነሳሽነታቸው  ከፍ እያለ ስለመምጣቱም ያመላክታል።

በእርግጥ የቀረጥ ነጻ እድሉ ከአገሪቱ እድገት ጋር ተያይዞ እየጨመረ መምጣቱ የሚጠበቅ ነው። የየዘርፉ ተዋንያንም እድሉን አሟጠው ለመጠቀም የሚያደርጉት ጥረት በጤናማነቱ ይወሰዳል። ይሁንና መንግስት የፈጠረውን መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው እድሉን የኪራይ ሰብሳቢነትና በአቆራጭ የመበልፀጊያ  ምንጭ ያደረጉ ጥገኛ ባለሀብቶች መፈልፈላቸው አሳሳቢ  እየሆነ መጥቶል ።

የዚህ ዝንባሌና ተግባር ማሳያ የሚሆኑ በርካታ ጉዳዮች ይነሳሉ። የቀረጥ ነጻ እድሉን በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠቀሙት አካላት  መካከል የኮንስትራክሽንና የቱሪዝም ዘርፎች  ተጠቃሽ ናቸው። መንግስት ለዘርፎቹ በሰጠው እድል የተለያዩ የግንባታ ቁሶችና ተሽከርካሪዎች  ያለ ቀረጥ ወደ  አገር ውስጥ ይገባሉ። ይሁንና ምን ያህሎቹ ለተገቢው አላማ እያዋሉት ነው የሚለው ሲፈተሽ  ኪራይ ሰብሳቢነቱ ሚዛን እየደፋ  ስለመምጣቱ   የሚጠቁሙ  መረጃዎች እውነታውን ገሃድ ያደርጉታል።

ለአብነት በ2008 በጀት አመት በስድስት ወራት ግምታቻው 50 ሚሊዮን ብር የሆኑ ከቀረጥ ነጻ የገቡ የግንባታ ዕቃዎች ያለአግባብ ጥቅም ላይ ሲውሉ መያዛቸውን የሚጠቁመው መረጃ ቆም ተብሎ መታሰብ እንዳለበት የሚያመለክት ነው። በቱሪዝምና በሌሎችም ዘርፉች ከቀረጥ ነፃ የገቡ ተሽከርካሪዎችና ማሽኖች  ለሌላ አላማ ሲውሉ በመገኘታቸው 10 ሚሊዮን ብር  ቀረጥና ታክስ እንዲከፍሉ መደረጉን የሚያሳየው  የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መረጃም  የማበረታቻ እድሉ በህገ ወጦች እየተጠለፈ ስለመሆኑ አቢይ ማሳያ ነው።

በቀረጥ ነጻ እድሉ ተጠቃሚ የሆኑትን አካለት በሙሉ በአንድ ቋት በመጨፍለቅ የህገ ወጡ ተግባር ተሳታፊ ናቸው  ማለት ግን አይቻልም። ይሁንና የጥቂቶች ራስ ወዳድነት የፈጠረው የኪራይ ሰብሳቢነት አባዜ ና ስራዉን የሚመሩና የሚያስፈፅሙ አንዳንድ ህገወጥ ተባባሪ የመንግስት አካላት  ድርጊት የሌሎችን ልማታዊ ባለሀብቶች አርአያነት ያለው ስራ ያደበዝዛል። ልማታዊ አካሄድንም ያዳክማል፡፡ ስለዚህም ጉዳዩ  ፈጣንና ጠንካራ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል።

የመፍትሄ ጉዳይ ሲነሳ በቅድሚያ ተዋናይ መሆን ያለባቸው በየዘርፎቹ የተሰማሩት አካላት ናቸው።  በዚህ ተግባር ስማቸው  ከሚጠቀሰው መካከል የኮንስትራክሽን፣ የኢንዱስትሪ ፣ የቱሪዝምና የሌሎችም ዘርፎች ባለድርሻዎች ያቋቋሟቸው ማህበራት ህገ ወጥ ተግባሩን በመከላከል ረገድ ሚናቸውን መወጣት አለባቸው።   ማህበራቱ በየሙያው የተሰማሩትንና በህገ ወጡ ተግባር የሚሳተፉትን አካላት ለመለየት የተሻለ ቅርበት ስላላቸው በህጋዊነት ከለላ የተሰገሰጉትን ኪራይ ሰብሳቢዎች በዋናነት  ማጋለጥ አለባቸው። አደረጃጀታቸውንም ህገ ወጥነትን ሊያመክን በሚያስችል ደረጃ ማዋቀር ይጠበቅባቸዋል።  ለእዚህም የሚገዛቸው የሙያ ስነምግባር ደንብ ከማዘጋጀት ባሻገር ሌሎችንም የመከታተያ እና የመቆጣጠሪያ ስልት በመንደፍ መንግስትን ሊያግዙ ግድ ይላቸዋል።

የቀረጥ ነጻ እድሉን ከመፍቀድ ጀምሮ ወደ አገር ውስጥ የገቡት እቃዎች በምን መልኩ አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ እስከመቆጣጠር ድረስ ባለው ሂደት ተሳታፊ የሆኑ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትም  ተግባራቸውን በቅጡ ሊፈትሹ ይገባል። መሬት ላይ በሌለ እውነታ ፈቃድ አውጥተው የእድሉ ተጠቃሚ በመሆን ለኪራይ ሰብሳቢነት የሚያውሉ አካላት ተግባር በአስፈጻሚ ውስጥ ከሚገኙ ተባባሪዎቻቸው ውጪ የሚሳካ  እንዳልሆነ ግንዛቤ ይዞ መታገልም ግድ ይላል። ወደ አገር ውስጥ ገብተው የሚደረገውን ቁጥጥር በማለፍ ተገቢ ላልሆነ አላማ ሲውሉ በጥቅም በመደራደር አጋዥ የሚሆኑት በመንግስት መዋቅር የተሰገሰጉ አጋሮች እጅ ስለሚገባበት ጥብቅ ክትትል ብሎም እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው።

ቅንጅታዊ ስራ የመፍትሄው አካል ሊሆን ይገባል። ስራው የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች የቁጥጥሩን፣ የክትትሉን እንዲሁም የወጡ ህጎችን ተግባራዊነት የሚገመግሙበት የጋራ መድረክ በማዘጋጀት  ሊሻሻሉ የሚገባቸውን የመፍትሄ አቅጣጫዎች ሊያስቀምጡ ይገባል።

መንግስት  ግብር በማስከፈልና ተገቢዉን ታክስ በመሰብሰብ የዜጎችን ህይወት ሊለውጥ የሚችል ከፍተኛ ገንዘብ ይቅርብኝ በማለት ለተቀደሰ አላማ ዋጋ ሲከፍል ህገ ወጦች የግል ካዝናቸውን ለመሙላት የሚጠቀሙበት ሁኔታ በጊዜ ካልተገታ አሉታዊ ጎኑ ይበዛል። የኢፍትሃዊነት በርም ይሰፋል፡፡  ልማታዊ ባለሀብቱን ያዳክማል፣ ህገ ወጥነት የበላይነት እንዲይዝ በር ይከፍታል፣  የስራ እድል እንዲፈጥሩ የታሰበላቸውን ዘርፎች ያቀጭጫል።  ስለዚህም የቀረጥ ነጻ እድሉ የተሰጠው ከከፍተኛ ኃላፊነት ጋር በመሆኑ ሁሉም  ተገቢውን ህጋዊ ግዴታውን ይወጣ። አሰራሩም ይጥበቅ ፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚውለውን 10 ቢሊዮን ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ በጀት ወደ ሥራ ለማስገባት አስፈላጊ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ባለፉት ስድስት ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ ያከናወናቸውን ዝርዝር ተግባራት ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በአዳማ ከተማ በመገምገም ላይ ይገኛል፡፡ በመድረኩ የተገኙት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳው፤ ለወጣቶች የተመደበውን ተዘዋዋሪ በጀት ወደ ሥራ ለማስገባት ክልሎች የበጀት መጠናቸውን እንዲያውቁ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በበጀቱ አጠቃቀም ዙሪያ ለፋይናንስ ተቋማት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መከናወኑን  ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ ይህም በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፍ የሚሰማሩ ወጣቶችን ከመደገፍ ባሻገር ‹‹የካፒታል ሊዝ ፋይናንስ›› እንዲሁም ለመካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚውል በየዓመቱ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ መመደቡ መንግሥት የወጣቱን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሻሻል እየሰራ ያለውን ሰፊ ሥራ እንደሚያመላክት ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ወጣቶች የአገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ መረዳት አለባቸው›› ያሉት አቶ ርስቱ፤ የታቀዱ ሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜ መሄድ ያልቻሉት ባለፉት ስድስት ወራት ከወጣቶች ጋር መመካከሪያ፣ ማደራጀትና መልሶ በማሰልጠን አሳልፈዋል፡፡

በመድረኩ የቀረበው ሪፖርት እንደሚያ መላክተው፤ የክልሎች የሥራ አፈጻጸም የተሟላ አይደለም፡፡ ‹‹በክልሎች መካከል የአፈጻጸም ወጥነት መጓደል በጀቱን በአግባቡ ወደ ሥራ ለማስገባት እንቅፋት አይሆንም?›› ለሚለው ጥያቄ፤ ክልሎች ወደ ቋንቋቸው በመቀየር ጭምር አስፈላጊ ዝግጅት ማድረጋቸውን በመጥቀስ በቀጣይ ድጋፉን አጠናክሮ ለመሄድ ሚኒስቴሩ በስፋት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በስድስት ወራት የዕቅድ ክንውን ግምገማ መድረክ የሚኒስቴሩ የስፖርት ዘርፍ እንዲሁም የወጣቶች ዘርፍ በተናጠል አፈጻጸማቸውን ፈትሸዋል፡፡ መድረኩ ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡ 

ብሩክ በርሄ                  

Published in የሀገር ውስጥ

የጤና ጣቢያው ከፊል ገጽታ እና ጉዳት የደረሰባቸው ንብረቶች፤

በየካ ክፍለከተማ የሚገኘው የየካ አባዶ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት አሥራ ሦስት ጤና ጣቢያ ህንፃ ግንባታ ከተጠናቀቀ አንድ ዓመት ሆኖታል። ከውጭ ሲታይ የጤና ጣቢያው ህንፃ ጥራቱን ጠብቆ መሰራቱን  ገፅታው ይመሰክራል። ወደ ህንፃው ውስጥ ሲገባ ግን በውጭ ከሚታየው  ተቃራኒ ነገር ያጋጥማል። ህንፃው ውስጥ የሚገኙ በሮች ተሰባብረው፣ እጀታቸው ተነቃቅሏል። መስታወቶቹና የመፀዳጃ ቤት ዕቃዎችም ከጥቅም ውጪ ሆነዋል።

ወጣት ብሌን ገብረስላሴ በየካ አባዶ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በፕሮጀክት አሥራ ሦስት ውስጥ መኖር ከጀመረች አጭር ጊዜ ሆኗታል። የቅርብ ዘመድ የሆነ ሰው እግሩ ላይ መስታወት ወድቆ ደም በከፍተኛ ደረጃ እየፈሰሰው ህክምና ቦታ ለማግኘት ተቸግረው እንደነበር ታስታውሳለች። አደጋ የደረሰበት ሰው የህክምና ተቋም ለማግኘት ራቅ ያለ ቦታ መሄድ ስለነበረበት ከፍተኛ ደም ፈሶት ራሱን ስቶ እንደደረሰ ትገልፃለች። «ጤና ጣቢያው አገልግሎት ቢሰጥ አንቸገርም ነበር» በማለት በቁጭት ትናገራለች፡፡

ወይዘሮ አቦነሽ ዳባ ከመጋቢት 2008 ዓ.ም  ጀምሮ በስፍራው መኖር እንደጀመሩና  ልጆቻችንን ለማስከተብ፣ ሲታመሙ ለማሳከም ሌላ አካባቢ መሄድ አለብን፤ ለተጨማሪ ወጪና ለእንግልት ተዳርገናል ይላሉ። ነፍሰ ጡር በነበሩበት ወቅትም የህክምና ክትትል ለማድረግ ወደ ሌላ አካባቢ ለመሄድ እንደተገደዱ ይናገራሉ። ሁለተኛ ልጃቸውን ሲወልዱም  ከፍተኛ ወጪ እንዳወጡና ህክምና  ለማግኘት እንደተንገላቱ ያመለክታሉ። እርሳቸውም «እዚሁ ግቢ ያለው ጤና ጣቢያ አገልግሎት ቢሰጥ ያለ ብዙ ወጪ መገላገል እችል ነበር» ይላሉ፡፡

ሌላው ነዋሪ  አቶ ኤልያስ ይፋቶ  እንደሚናገሩት፤  የነዋሪዎቹን አቤቱታ በመያዝ በተደጋጋሚ ለክፍለ ከተማው ጤና ቢሮና ሥራ አስፈፃሚው ቢሮ ደጅ ቢጠኑም ለአንድ ዓመት ያህል መፍትሄ ማግኘት አልቻሉም። ወደሚመለከታቸው ኃላፊዎች ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ «በቅርቡ ይሰራል፣ ሥራ ይጀምራል ሌሎች ችግሮችንም ለመፍታት እየሰራን ነው» በማለት ጥሩ ምላሽ ይሰጣቸዋል። ይሁንና እስካሁን መፍትሄ  አላገኙም፡፡

ነዋሪዎቹ እንደሚናገሩት ጤና ጣቢያው እስከ ሐምሌ 2008 ዓ.ም ድረስ ጥበቃ አልነበረውም። ይህ ስላሳሰባቸው ጥበቃ እንዲቀጠር በተደጋጋሚ በመጠየቃቸው ቢቀጠርም ዘግይቶ የጤና ጣቢያው ንብረት በተለያየ ምክንያት ከወደመ በኋላ ነው። በሌላ በኩል እንደ መንገድና ሌሎች መሰረተ ልማት በአቅራቢያው አለመገንባቱ ችግር መፍጠሩን እንዲሁም የጎርፍ ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ይህንን ችግራቸውን አቤት የሚሉበት የወረዳ  አስተዳደር በአቅራቢያቸው አለመኖሩ ደግሞ ችግራቸውን አባብሶታል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ የጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሲስተር ሙሉ ተካ ጤና ጣቢያው ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ይናገራሉ። ‹‹የነዋሪዎቹን ጥያቄ በተደጋጋሚ ቢቀርብም የህንፃው ግንባታ በጊዜው አላለቀም ነበር። አምና ተከስቶ የነበረውን የአተት በሽታ  መቆጣጠር  ላይ ነበር ትኩረታችን›› ይላሉ፡፡ በጤና ጣቢያው ህንፃ ላይ የደረሰው ውድመት ህንፃውን ከተረከቡ በኋላ እንደሆነ ግን ያምናሉ፡፡ የደመወዝ ክፍያው አነስተኛ በመሆኑ  በወቅቱ ጥበቃ ለመቅጠር አለማስቻሉን  ይናገራሉ።

ጤና ጣቢያው ተገንብቶ ካለቀ በኋላ ለምን አገልግሎት እንዳልጀመረ ሲጠየቁም ‹‹ጤና ጣቢያው የመብራትና የውሃ አገልግሎት አልተዘረጋለትም። የመብራት ዝርጋታ ችግሩ ትራንስፎርመር አገር ውስጥ ያለመኖር ችግር ነው። ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተወሰኑ እቃዎችን የማሟላት ሥራ ተሰርቷል›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ጤና ጣቢያው እስካሁን ሥራ መቼ እንደሚጀምር ሲመልሱም ‹‹እየሰራን ነው፣ ወደ 13 የህክምና ባለሙያ ቀጥረን በሌላ ጤና ጣቢያ እየሰሩ ይገኛሉ፣ በቅርቡ ትራንስፎርመር ወደ አገር ይገባል፣ ወንበርና ጠረጴዛ የመሳሰሉትን ገዝተናል፣ እነዚህን የሚከታተል አካል ተመድቦ እየሰራ ነው›› ብለዋል፡፡ አክለውም የጤና ጣቢያው ህንጻ በየካቲት ወር መጨረሻ  ተጠግኖ ያልቃል የሚል ተስፋ ሰጥተዋል፡፡ 

በሌላ በኩል ደግሞ ኃላፊዋ እንደተናገሩት፤ ነዋሪው በቅርብ ጤና ጣቢያ ተገንብቶ እያለ ወደ ሌላ ቦታ ለምን እንሄዳለን በሚል ካልሆነ በስተቀር ብዙም ርቀት የሌለው የጤና ተቋም ስላለ በእዚያ  መጠቀም ይችላል፡፡

የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር  ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተሾመ መንገሻ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ነዋሪዎች የሚያነሱት ቅሬታ ትክክል ነው። ተገንብቶ ያለቀው ጤና ጣቢያ አገልግሎት መስጠት ነበረበት። በቅርቡ ከተጠባባቂ በጀት ለጤና ጣቢያው ዕድሳት እንዲደረግ ተወስኗል። የተረከቡት ግንባታቸው ያልተጠናቀቀ ህንጻ ነው። ከከፍታ ቦታ የሚመጣው ጎርፍ የነዋሪዎቹ ቤት እየገባ መቸገራቸውን ባቀረቡት ቅሬታ መሰረት እንዲስተካከል ተሞክሯል። ይሁንና  በቂ አይደለም።

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን ጉዳያቸውን አቤት የሚሉበት የቅርብ የወረዳ አስተዳደር ባለመኖሩ በቀጥታ ወደ ክፍለ ከተማ ለመሄድ መገደዳቸውን በተመለከተም «የወረዳ አስተዳደር መኖር እንዳለበት ብናውቅም ችግሩን ክፍለ ከተማው ሊፈታው አይችልም። በጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ውስጥ ያሉት ጉድለቶችና ችግሮች የሚያስፈፅማቸው አካል የተለያየ በመሆኑ ነው ለመፍታት ያስቸገረው›› ብለዋል።

ዜና ሐተታ

ሰላማዊት ንጉሴ

Published in የሀገር ውስጥ

በኦሮሚያ ክልል የመልካም አስተዳደር ችግር በመፍጠር፥ በኪራይ ሰብሳቢነትና በአቅም ማነስ የተነሳ 4ሺ 460 ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ከኃላፊነት መነሳታቸው ተገለጸ።

የክልሉ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ትናንት  በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የክልሉ መንግሥት  ከህዝብ ቅሬታ በመነሳት ባደረገው ግምገማ 4ሺ 460 ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮችን ከኃላፊነት አንስቷል። ከአመራሮቹ መካከል 2ሺ 587 በአቅም ማነስ፣ 964 በሙስና፣ 397 በሥነ ምግባር ችግር እንዲሁም 512  ያህሉ ደግሞ በተለያየ ምክንያት ከአመራርነት የተነሱ ናቸው።

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፤ በግምገማው ወቅት ችግሮችን ነቅሶ የማውጣት ብቻ ሳይሆን በተፈጠረው ችግር ላይ የኔ ድርሻ ምንድነው? በማለት አመራሩ ራሱን እንዲያይ ተደርጓል፡፡ለየተፈጠረው ችግር ከከፍተኛ  እስከ ታችኛው  አመራር ድረስ ክፍተት እንደነበረበት ተገምግሟል። በፍትህ አካላት የሚታየው የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ሙሰኝነትና የዴሞክራሲያዊነት መጓደል  የህብረተሰቡን ቅሬታ ከፈጠሩት ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

 ከፐብሊክ ሰርቪሱ አኳያ የአገልጋይነት ስሜት መጓደል፣ የለውጥ ትግበራ መሳሪያዎችን በአግባቡ ተግባራዊ ያለማድረግ፣ የመንግሥት ፖሊሲዎችን የማስፈፀም አቅም ውስንነት፣ የተገልጋዩን እርካታ በማረጋገጥ አገልግሎትን ከመስጠት አኳያ ክፍተት መኖር እንደ ችግር  መነሳቱን አቶ አዲሱ አስረድተዋል፡፡ አመራሮቹ ከህዝብ የተሰጣቸውን ስልጣን ለግል ጥቅም በማዋል ከህዝብ የኑሮ ደረጃ በላይ የመኖር፣ የህዝብን ችግር በአግባቡ ያለማዳመጥ እና ከህዝብ የመነጠል ሁኔታዎች እንዳሉም ታውቋል።

የክልሉ ካቢኔ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ በአዲስ መልክ እንዲደራጅ ተደርጓል። በተደረገው አደረጃጀት መሠረት 5ሺ 832  አዳዲስ አመራሮች ተተክተዋል። አዲስ የተሾሙት አመራሮች በትምህርት ደረጃ፣ በሥራ ተነሳሽነትና በፖለቲካዊ አመራር ብቃታቸው ታይቶ እንደሆነም ተገልጿል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ በግምገማው መሠረት የህግ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው በሂደት ላይ የሚገኙ በሙስና ከተገመገሙ 964 አመራሮች መካከል 260ዎቹ  ላይ ክስ በመመሥረት በህግ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ። በቀሪዎቹ ላይ መረጃ የማጣራት፣ የማሰባሰብና ክስ የመመሥረት ሂደት ላይ ይገኛል። በተጨማሪም እንከአሁን ባለው ሂደት በፍርድ ቤት የታገዱ ንብረቶች ይገኛሉ። 7ሚሊዮን 149 ሺ 103 ብር፣ አራት ተሽከርካሪዎች፣ 40መኖሪያ ቤቶች፣ ሁለት ሕንፃዎች፣ 244ሺ 356 ካሬ ሜትር የከተማ ቦታና፣ 54ነጥብ86 ሄክታር በደን የተሸፈነ መሬት እንዲታገድ ተደርጓል።

ከህዝብ የተመዘበሩት ንብረቶች እነኚህ ብቻ እንዳልሆኑ  ገልጸው፤ የታገዱት ንብረቶች የፍርድ ሂደቱ ሲያልቅ ለህዝብ አገልግሎት እንደሚውሉ ጠቁመዋል፡፡ በአጠቃላይ በክልሉ በግምገማው 6ሚሊዮን 476ሺ  295 ህዝብ  ተሳትፏል፡፡

ሰላማዊት ንጉሴ

 

Published in የሀገር ውስጥ

ምንጭ ፡- የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን    ዓመተ ምህረት

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መረጃ እንደሚያመለክተው በ2008 በጀት ዓመት ለተለያዩ ዘርፎች በተሰጠው የቀረጥ ነፃ ዕድል የ 71 ቢሊዮን ብር ዕቃዎች ከውጭ ገብተዋል። ይህም ከ2007 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የስምንት በመቶ ዕድገት አሳይቷል። በሌላ በኩል  የባለስልጣኑ የኢንተለጀንስ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ይበልጣል አየለ  በ2008 በጀት ዓመት  በቱሪዝምና በሌሎችም ዘርፉች ከቀረጥ ነፃ የገቡ ተሽከርካሪዎችና ማሽኖች  ለሌላ ዓላማ ሲውሉ በመገኘታቸው 10 ሚሊዮን 216 ሺ ብር ቀረጥና ታክስ እንዲከፍሉ መደረጉን አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የካቲት 10 ቀን 2008 ዓ.ም ያወጣው ዜና እንደሚያመለክተውም፤ ባለፈው በጀት ዓመት ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ከቀረጥ ነፃ የገቡ የግንባታ ዕቃዎች ያለአግባብ ጥቅም ላይ ሲውሉ ተይዘዋል።

የተጠቀሱት መረጃዎች የቀረጥ ነፃ ዕድሉ እያደገ ቢመጣም  ለሌላ ዓላማ እየዋለ መሆኑን ያመለክታሉ፤ የችግሩ ስፋት ምን ይመስላል? መፍትሔውስ ?  

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የእቅድና አፈፃፀም ዳይሬክቶሬት የማክሮ መረጃ ከፍተኛ ኦፊሰር  አቶ ታምራት አኒሴ እንደሚያብራሩት፤  መንግሥት በ2008 በጀት ዓመት ከታክስና ከቀረጥ ያገኘው ገቢ 144 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ነው። ይህም ካለፉት ዓመታት አኳያ የተሻለ ቢሆንም ያለቀረጥ ነፃ በገቡ ዕቃዎች የገቢውን ግማሽ በመቶ ያህል አሳጥቶታል። «ለተለያዩ ሥራዎች ሊውሉ  የሚችሉ ከውጭ የገቡ ዕቃዎች   ለታለመላቸው ዓላማ አለመዋላቸው ኢኮኖሚውን ይጎዳዋል» ይላሉ፡፡

 ይህ ሁኔታ በአጠቃላይ በአገሪቱ  ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳርፍ አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ምሁራን ያምናሉ፡፡ አቶ ታረቀኝ አያሌው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በንግድ ሥራ ትምህርት ቤት የአካውንቲንግና የንግድ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና መምህር ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደ ሚናገሩት፤ መንግሥት በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ለማበረታታት የቀረጥ ነፃ ዕድል መፍቀዱ ተገቢ ነው፡፡ ዘርፉን ከማበረታት ባሻገር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለማስቀረትና ሠፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል፡፡ ይህ በሌሎች አገራትም የሚተገበር ስትራቴጂ ነው፡፡

 «ይሁንና ማበረታቸው ለታለመለት ዓለማ አለመዋሉ ፍትሐዊ የሆነ ውድድር እንዳይኖር ያደርጋል፤ መንግሥትም ለልማት ያውለው የነበረውን ከፍተኛ ገቢ በማሳጣት ኢኮኖሚውን የሚያንቀ ሳቅስበት አቅሙን ያቀጭጨዋል» ይላሉ፡፡  በህጋዊ መንገድ 

የሚሠራውን ባለሀብት አቅም እንደ ሚያዳክምና በዜጎች መካከል የሀብት ክፍፍሉም ፍትሐዊነት እንዲጎድለው የሚያደርገው መሆኑን ነው የሚያስረዱት፡፡ በተጨማሪም  እንደታሰበው የሥራ ዕድል ባለመፈጠሩም አኩራፊ ዜጎችን በማበራከት በመንግሥትና በህዝብ መካከል መቃቃር  እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል ባይ ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በንግድ ሥራ ትምህርት ቤት የአካውንቲንግና የንግድ አስተዳደር ትምህርት ክፍል  መምህር የሆኑት አቶ ግርማ ዳኜ በአቶ ታረቀኝ ሃሳብ ይሰማማሉ፡፡ «ይህ ሁኔታ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳርፈው አሉታዊ ተፅእኖ አያጠያይቅም» ይላሉ፡፡ በተለይም ምርቶቹ ቀረጥና ታክስ ተከፍሎባቸው  አለመግባታቸው መንግሥት  ለልማት  ከፍተኛ የፋይናስ አቅም እንዳያገኝ ማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ ህዝቡም ከልማቱ እንዳይቋደስ እክል እንደሚፈጥር ያስረዳሉ፡፡  በተጨማሪም ህገወጥነትን በማስፋፋት ቀውስ እንደሚያስከትል ነው የሚጠቁሙት፡፡

ይህ ሁኔታ ሊፈጠር የቻለበትን  ምክንያት ሲያስረዱም  የኢኮኖሚ ምሁራኑ ያተለያዩ  መላምቶችን ያስቀምጣሉ፡፡ አቶ ግርማ እንደሚሉት፤ የቀረጥ ነፃ ዕድሉን በአግባቡ  ያልተጠቀሙ ባለሀብቶች ሲጀመርም  የንግድ ፍቃድ ያወጡበት ዓለማ ለማልማት ላይሆን ይችላል፡፡ ከዚያ ይልቅም መንግሥት የፈጠረውን ምቹ ዕድል በመጠቀም አላግባብ ለመክበር ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ቀድሞ የተመዘገበበት ዘርፍ አላዋጣ ሲለው ወደሌላ ሲሸጋገር  የተጠቀመውን ነፃ ዕድል የመመለስ ወይም ቀረጥና ታክስ ለመንግሥት መክፈል እንዳለበት ካለማወቅ ይፈጠራል።

ይህ ሁኔታ ከአልጠግብ ባይ አስተሳሰብ የመነጨ እንደሆነ የሚናገሩት ደግሞ አቶ ታረቀኝ አያሌው ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው እምነት፤ የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው አብዛኞቹ ሰዎች ባገኙት ቀዳዳ ሁሉ አለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌ ይስተዋልባቸዋል፡፡ ይህም በዋናነት የአመለካከት ችግርን ስለሚያሳይ አስተሳሳብ ቀረፃ ላይ የተሠራው ሥራ በቂ አለመሆኑን ይጠቁማል።

ሁሉቱም ምሁራን በአንድ ነገር ይስማማሉ፡፡ ይኸውም ለችግሩ መፈጠርም ሆነ መባባስ ዋና ተጠያቂ ሊሆን የሚገባው መንግሥት መሆኑን ነው፡፡ ለዚህ አባባላቸውም  በዋናነት ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት አለመበጀቱ፥ የህግ ማዕቀፍ አተገባበር ክፍተትና መንግሥታዊ ተቋማት ተቀናጅተው ያለመሥራ ታቸውን በምክንያትነት ያስቀምጣሉ፡፡

 የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የኢንተለጀንስ ዳይሬክተር ተወካዩ አቶ ይበልጣል  በባለሙያዎቹ ሃሳብ በከፊል አይስማሙም፡፡ በተለይም የቁጥጥር ስርዓት አልተበጀም፤ ህጉ በአግባቡ አልተተገበረም የሚሉትን ሃሳቦች ይቃወማሉ፡፡ ለዚህም ዋቢ የሚያደርጉት መንግሥት የቀረጥ ነፃ ዕድልን አላግባብ የሚጠቀሙ አካላትን እንዲቆጣጠር ለባለስልጣኑ መብት መስጠቱን ሲሆን፤ ባለስልጣኑም እነዚህን አካላት ለመቆጣጠር የሚያስችሉትን መመሪያዎች ከመቅረፅ ባለፈ ይህንን ጉዳይ ብቻ የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ዳይሬክቶሬት ለማቋቋም እየጣረ መሆኑን ነው፡፡

 «የጉምሩክ አዋጅ 859/ 2006 ላይ በአንቀፅ 163ና 164 እንዲሁም መመሪያው ቁጥር 78/2004 አንቀፅ 18   በጊዜያዊነትም ቢሆን   ከቀረጥ ነፃ ገብተው ለታለመላቸው ዓላማ  ሳይውሉ ሲቀሩ ወይም በሌላ ሰው ይዞታ ስር ቢገኙ ቀረጥና ታክስ እንዲከፍሉ ይደነግጋሉ» ሲሉም አቶ ይበልጣል ያስታውሳሉ፡፡ እነዚህን መመሪያና ደንቦች መሠረት በማድረግም ዳይሬክቶሬቱ የቁጥጥር ሥራ እየሠራ መሆኑን በዚህ ተግባር ሲሰማሩ የተገኙትን አካላት ከቀረጥና ታክሱ በተጨማሪ ዕቃው ሊያወጣ ከሚችለው 50 በመቶ እንደሚከፍሉ ያመለክታሉ፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በለስልጣኑ በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ለማደን ያስችለው ዘንድ ለጠቋሚዎች ወሮታ መክፈል የሚያስችል ደንብ አዘጋጅቷል፡፡ በዚህም መሠረትም ህብረተሰቡን በጥቆማ ሰጪነት ለማሳተፍ ለጠቋሚ 20 በመቶ፣ ድጋፍና ክትትል ላደረጉ አካላት 10 በመቶ እንዲሁም  ለህግ አስከባሪ ተቋማት ደግሞ 30 በመቶ ይከፈላል፡፡

ከባለድርሻ አካላት ጋር ተናቦና ተቀናጅቶ የመሥራቱ ጉዳይ የሚፈለገውን ያህል አለመሆኑ ላይ አቶ ይበልጣል ይስማማሉ፡፡ በተለይም ባለስልጣኑ ብቻውን ህገወጥነትን ሊከላከል ስለማይችል ተቋማትም ሆኑ ህብረተሰቡ ጥቆማ ከመስጠት ጀምሮ ድጋፍቸው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ነው ያሰመሩበት፡፡

የኮንስትራክሽን ዘርፍ አንቀሳቃሽ ባለሀብቶች በቀረጥ ነፃ መብቱ አላግባብ ይጠቀማሉ ተብለው ከሚታመኑ መካከል ናቸው፡፡ ይህንን በሚመለከት የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ስለሺ ዘገየ ተጠይቀው «ሚኒስቴሩ በመንግሥት የተሰጠው ኃላፊነት የዘርፉን አንቀሳቃሾች የመደገፍና የማብቃት ሥራ ነው፤ ከዚህ ውጪ የተሰጣቸውን ዕድል አላግባብ የተጠቀሙ አካላትን ሰዶ የማሳደድ   ሥራ አይሠራም» ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

 እርሳቸው ይህን ቢሉም ህገወጥነትን የመከላከል የማንኛውም መንግሥታዊም ሆነ የሌሎች አካላት ኃላፊነት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ ያላቸውን አስተያየት ሲሰጡም «ሁሉም የራሱ የሆነ ድርሻ አለው፤ ይህንን ጉዳይ የሚከታተሉት በየክልሉና ከተማ አስተዳደር ያሉ አካላት ናቸው፡፡ ስለቁጥጥሩም መረጃ ማግኘት የሚቻለው ከእነዚህ አካላት ነው» ብለዋል፡፡  በሌላ በኩል ግን በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተቋቋሙ ማህበራት በአንዱ ጥፋት ሁላችንም መወቀስ የለብንም በሚል ደንብ አዘጋጅተው አባላቶቻቸውን የሚቆጣጠሩበት ሁኔታ መኖሩን ነው የጠቆሙት፡፡

በሚኒስቴሩ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኝነት ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ናሆም በላቸው  እንደተናገሩት፤ ሚኒስቴሩ ህገወጦችን ለመቆጣጠር የሚያስችል የኮንስትራክሽን ኦዲት ረቂቅ መመሪያ የማዘጋጀት ሥራ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ዘርፉን አስቀድሞ ማጠናከር ይገባል በሚል መመሪያው እንዲዘገይ መደረጉን ጠቁሟል፡፡ ስለመመሪያው አጠቃላይ ይዘት ማብራሪያ ለመስጠት ግን በረቂቅ ደረጃ ያለ በመሆኑ እንደማይቻል አመልክተዋል፡፡ 

ምሁራኑ እንደተናገሩት፤ መንግሥት የፈጠረውን ምቹ ዕድል ከህገወጦች መታደግ የሚቻለው በዋናነት ቁጥጥሩን በማጠናከር ነው፡፡ ለዚህ ደግም አቅምን በላቀ ደረጃ ማሳደጉ አያጠያይቅም፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራም በስፋት መሥራት አለበት፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ጠንካራ የሆነ መመሪያና አስተማሪ የሆነ ዕርምጃ መውሰድም ይጠይቃል፡፡ የቁጥጥሩ ሥራም መጠናከር አለበት። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን ህገወጥነቱ አሁን ካለውም በላይ በአገሪቱ ይነግሣል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችን የማባባስ ዕድል ይኖረዋል። መንግሥት የጀመራቸውን የልማት ሥራዎች ለማስቀጠልም በሚያደርገው ጥረት ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽእኖ ያሳርፋል።

ዜና ትንታኔ

ማህሌት አብዱል

 

Published in የሀገር ውስጥ

ከሁለት ስኳር ፋብሪካዎች በዘጠኝ ዓመት የቀረበው 60 ሚሊዮን ሊትር ኤታኖል ከነዳጅ ጋር ተደባልቆ 50 ሚሊዮን ዶላር ማዳን ቢያስችልም ካለፈው ዓመት ጀምሮ  አቅርቦቱ መቋረጡን የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የባዮፊውል ልማት ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ሚካኤል ገሰሰ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለጹት፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የኤታኖል ምርት አቅርቦት ባይቋረጥ እስከ 20 ሚሊዮን ሊትር ከውጭ የሚገባ ነዳጅን ይተካ ነበር፡፡ መንግሥት ሥራውን ሲያስጀምር ለነዳጅ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ከመቀነስ በተጨማሪ የአየር ንብረት ብክለትን መከላከል የሚሉ ሁለት ጉዳዮችን ታሳቢ ነው፡፡

ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ ስትራቴጂ ወጥቶ ነዳጅን ከኤታኖል መቀላቀል የተጀመረ ቢሆንም  ‹‹የባዮፊውል ፖሊሲ›› ስላልተቀረፀለት በበላይነት የሚቆጣጠረው አካል እንደሌለ አቶ ሚካኤል ጠቁመዋል። ‹‹ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይሄን ለመቆጣጠር ኃላፊነት አልተሰጠውም›› በማለት ስኳር ፋብሪካዎችን ‹‹ለምን ኤታኖል አላመረታችሁም?›› በሚል ለመጠየቅ የሚያስችል የሕግ መሰረት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

‹‹ስኳር ፋብሪካዎቹ አቅርቦቱን በማቋረጣቸው ካለፈው ዓመት ጀምሮ የኤታኖል ድብልቁ ተቋርጧል›› የሚሉት አቶ ሚካኤል፤ በዚህ ምክንያት አገሪቱ የምታገኘውን ከፍተኛ ጥቅም አጥታለች፡፡   

በስኳር ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም ፤ አቅርቦቱ የተቋረጠው በመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ‹‹ኤታኖል ፕላንት›› ካጋጠመው የማሽን ብልሽት ጋር በተያያዘ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በአገሪቱ ካሉት ስኳር ፋብሪካዎች የኤታኖል ምርት የሚያቀርቡት ፊንጫ እና መተሃራ ስኳር ፋብሪካዎች ብቻ መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ ጋሻው ፤  የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ «የኤታኖል ፕላንት» አሁንም ቢሰራም፤ እንደ አገር ካለው ሰፊ ፍላጎት አንጻር መጠኑ በቂ ባለመሆኑ አቅርቦቱ ለመቋረጥ መቻሉን አመልክተዋል፡፡

ኤታኖል ከቤንዚን የመደባለቁ ሥራ ከአስር ዓመት በፊት በዓለም የነዳጅ ዋጋ ማሻቀቡን ተከትሎ የተጀመረ  ነበር፡፡ በዚህ ወር መግቢያ የነዳጅ ዋጋ ባለፈው ወር ከነበረው አንጻር ጭማሪ በማሳየቱ በትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ማሻሻያ መደረጉም ይታወሳል፡፡

Published in የሀገር ውስጥ

 

ኢህአዴግን ጨምሮ 22የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ የድርድርና የውይይት ረቂቅ ደንብ ለማዘጋጀት ስምምነት ላይ በመድረሳቸው ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወክሉ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ መሰየሙ ተገለጸ።

ከተመረጡት አምስቱ የፓርቲዎቹ  ቃል አቀባይ ተወካዮች አንዱ የሆኑትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበራት ጉዳዮች አስተባባሪ ሚኒስትር አቶ አብዱልአዚዝ መሐመድ ትናንት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ የውይይት መድረክ ከተካሄደ በኋላ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ ከ22ፖለቲካ ፓርቲዎች በተወከሉ ሰባት አባላት የውይይትና የድርድር አካሄድ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ  እንዲቀርብ ስምምነት ላይ በመድረሳቸው ቀጣይ ስብሰባው የካቲት17 ቀን2009ዓ.ም እንዲሆን ተወስኗል።

ሃያ ሁለት አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥር 10 ቀን 2009ዓ.ም ባደረጉት የመጀመሪያው ስብሰባ ላይ በደረሱት ስምምነት 20ፓርቲዎች የድርድሩንና የውይይቱን  አካሄድ በተመለከተ  የመነሻ ሃሳቦቻቸውን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጽሑፍ ማቅረባቸውን አቶ አብዱልአዚዝ አስታውሰው፤  ከእያንዳንዱ ፓርቲ የቀረበ የመነሻ ሃሳብ ላይ ሠፊ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።

በዕለቱ የተካሄደውን ስብሰባ  የትኛው ፓርቲ ይምራው በሚለው ጉዳይ ላይ በተደረገው ውይይት  ኢህአዴግ እንዲመራው ስምምነት ላይ በመደረሱ እንዲመራው መደረጉን አቶ አብዱልአዚዝ ገልጸው፤ በቀጣይ የሚካሄደውን የውይይት መድረክ ማን እንደሚመራው በፓርቲዎች ስምምነት የሚወሰን መሆኑን አመልክተዋል።

ከአምስቱ የፓርቲዎቹ  ቃል አቀባይ ተወካዮች አንዱ የሆኑት የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት  አቶ ትግስቱ አወሉ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ፓርቲዎች በግልም ሆነ በቡድን ያቀረቡትን የተለያዩ የውይይትና የድርድር አካሄድ ነጥቦች (ሞዳሊቲዎች) ወደ አንድ በማሰባሰብ   የሁሉንም ፓርቲዎች ሃሳብ አካቶና ሌላም ካለ ጨምሮ የተሟላ የድርድርና የውይይት አካሄድ ረቂቅ ደንብ በማዘጋጀት በመጪው ሳምንት በሚካሄደው ስብሰባ ይቀርባል። ውይይት ተደርጎበት ስምምነት ላይ ከተደረሰ ይጸድቃል። ሰባቱ የተወከሉ አባላትም ይህንን ረቂቅ ደንብ በባለሙያዎች ታግዘው ያዘጋጃሉ።

ሃያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ካቀረቡት የውይይትና የድርድር መነሻ ሃሳቦች በ12 ነጥቦች መካከል የድርድሩና የክርክሩ ዓላማ፣ተሳታፊዎች፣የሚዲያ አጠቃቀም፣ የንግግርና የተናጋሪዎች አሰያየም እና የጋራ ፎረሙ አባላትና ታዛቢዎችን የተመለከቱ ጉዳዮች እንደሚገኙበት ተጠቅሷል። ረቂቅ ደንቡን ለማዘጋጀት ከተመረጡት መካከልም ኢህአዴግ፣ መድረክ፣ መኢብን፣ ኢዴፓና ሰማያዊ ፓርቲዎች እንደሚገኙበት ተጠቅሷል።

 

ጌትነት ምህረቴ

 

Published in የሀገር ውስጥ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።