Items filtered by date: Friday, 17 February 2017

የቀድሞው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች እና የእግር ኳስ ተንታኝ ጋሪ ኔቭል  ቼልሲ በቀጣይ ጨዋታዎች ነጥብ የሚጥልበት አጋጣሚ ቢኖርም፤ ተፎካካሪ ክለቦች ግን የነጥብ ልዩነቱን ለማጥበብ እንደሚቸገሩ ተናገረ። በሌላ በኩል ደግሞ የቼልሲ ክለብ የመስመር ተጫዋች የሆነው ፔድሮ አሁንም ድረስ  ክለቡ ከተፎካካሪዎቹ ያለውን የስምንት ነጥብ ርቀት አስጠብቆ ለመጓዝ ሠፊ ዕድል እንዳለው ገልጿል።

ጋሪ ኔቭል ቼልሲን ለማቆም እየተጣጣሩ ያሉትን ማንችስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል፣ አርሰናል እና ቶተንሀምን ተስፋ የሚያመነምን አስተያየቱን ሲሰጥ «አሁን ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ ነው። ቼልሲን ለማቆም በቀጣይ ታሪካዊ የሆነ  እንቅስቃሴ ማድረግ የሚጠይቅ ነው» በማለት ቀሪ ጨዋታዎችን በጥንቃቄ አሸንፎ ቼልሲ ነጥብ እንዲጥል መጠበቅ በጣም ከባድ ጉዞ ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል።

ሰማያዊዎቹ ተከታታይ 13 ጨዋታዎችን በማሸነፍ ሊጉን በሠፊ የነጥብ ልዩነት መምራት ችለዋል። እስከአሁን ድረስ ቼልሲን በነጥብ የቀረበው ክለብ አልተገኘም። ባሳለፍነው ሳምንት ከበርንሌ ጋር አቻ  በመውጣቱ ሁለት ነጥቦችን መጣል ችሎ ነበር። በዚህም ማንችስተር ሲቲ ተጋጣሚውን በመርታት ከመሪው ጋር ያለውን ልዩነት 8 ሊያደርሰው ችሏል። በቀጣይ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት 13 ጨዋታዎች ይቀራሉ። በዚህም ቼልሲ ከባድ ጨዋታዎች ያጋጥሙታል። በድል መወጣት የሚችል ከሆነ እና ያለው የነጥብ ልዩነትም አስጠብቆ የሚቆይ ከሆነ ግን ዋንጫውን የማያነሳበት ምክንያት አይኖርም።

 ማንችስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል፣ አርሰናል፣ ቶተንሀምን እና ማንችስተር ዩናይትድ ቼልሲ ነጥብ ጥሎ ልዩነታቸውን ለማጥበብ የሚችሉበትን አጋጣሚ እየተጠባበቁ ቢሆንም በእጃቸው ያለውን ዕድል በተደጋጋሚ ሲያባክኑ ቆይተዋል። ለ8 ጊዜያት የፕሪሚየርሊጉን ዋንጫ ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ማንሳት የቻለው ጋሪ ኔቭል ለስካይ ስፖርት በሰጠው አስተያየት « እኔ ቼልሲ ነጥብ እየጣለ ተፎካካሪዎቹ ደግሞ ልዩነቱን እያጠበቡ ይመጣሉ የሚል ግምት የለኝም። ቼልሲን ለማቆም እነዚህ ክለቦች በተከታታይ 13 እና 14 ጨዋታዎችን ማለትም የቀሩትን ሁሉንም ጨዋታዎች ማሸነፍ ይኖርባቸዋል። ቼልሲ ግን 3 እና አራት ጨዋታዎችን ቢሸነፍም በተከታታይ በርካታ ጨዋታዎችን በዚህ ዓመት ሲያሸንፍ ማየት ችለናል። በእኔ ግምት ሌሎች ክለቦች በዚህ የውድድር ዓመት የሚደግሙት አይመስለኝም።

«በዘንድሮው ዓመት የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ቼልሲ ተመራጭ ክለብ ነው። ነገር ግን ቁልፍ ተጫዋቾቹን ሊያጣ የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩ ሀቅ ነው። ይህ ድሉን እንዳያጣጥም እንቅፋት ሊሆነው እንደሚችልም ጥርጥር የለውም። ሆኖም ግን አጋጣሚው ሊከሰትም ላይከሰትም የሚችል ነው። በዚህ የተነሳም ሠፊ ዕድል አለው» ማለቱ የኔቭል ግምት ወደ ቼልሲ አዘንብሏል።

ሰማያዊዎቹ በያዝነው ዓመት ለሦስት ጊዜ ብቻ ነው ሽንፈት ያጋጠማቸው። ከአጠቃላይ 25 ሳምንቶች ውስጥ ደግሞ 19ኙን በድል አጠናቀዋል። በጠንካራ የተከላካይ ስብስብ የሚጠበቀው የግብ መስመራቸውም ጥቂት ጎሎችን ነው ያስተናገደው።

በተመሳሳይ ዜና ቼልሲ ያሳለፍነውን ሳምንት ጨዋታ ከበርንሌይ ጋር ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱን ተከትሎ፤ የአቻነቷን ግብ ያስቆጠረው የመስመር ተጫዋቹ ፔድሮ «አሁንም ዋንጫውን ለመብላት እና በሠፊ የነጥብ ልዩነት ሊጉን ለመምራት ዕድል አለን» በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል። ቼልሲ ከበርንሌይ ጋር ያሳለፍነው ዕሁድ ብዙም የማያስደስት የጨዋታ ጊዜ ነው። የላንክሻዬሩ ክለብ በርንሌይ የቼልሲን የግብ ክልል ሲፈትሽ አምሽቷል። ዕለቱ ብርዳማና ዝናባማ ስለነበር ለቼልሲ ተጫዋቾች ጨዋታውን ከባድ አድርጎባቸው ነበር።

ያሳለፍነው ሰኞ ዕለት ማንችስተር ሲቲ ቦርንማውዝን 2ለ0 ካሸነፈ በኋላ ከቼልሲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ8 አውርዶታል። ሆኖም ግን ፔድሮ አሁንም ከምንም ጊዜ በተሻለ ድሉ የኛ ነው የሚል አስተያየቱን ሰጥቷል። «በተቻለን አቅም በጣም ጥቂት ነጥቦችን ብቻ ነው መጣል የሚኖርብን። አሁንም ዕድሉ አለን። ነገር ግን በእንግሊዝ ሊግ ቀድሞ ዋንጫውን ይሄኛው ክለብ ይበላዋል ብሎ ለመገመት በጣም ከባድ ነው። እንደሚታወቀው በጣም ከባድ ተፎካካሪዎች ናቸው ያሉን። ማንችስተር ሲቲ፣ቶተንሀም እና ሊቨርፑል ጠንካራ ክለቦች ናቸው። እኛም ግን ከነርሱ በተሻለ ጥንካሬ ላይ እንገኛለን» ሲል ተናግሯል።

 ፔድሮ በዘንድሮው ዓመት ለቼልሲ 9 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ባሳለፍነው ዓመት ተጫዋቾች 8 ግቦችን ብቻ ነበር ማስቆጠር የቻለው። በአጠቃላይ ከባርሴሎና ወደ ቼልሲ ከመጣ ጀምሮ 50 ግቦችን በስሙ ማስመዝገብ ችሏል። እንደ ፔድሮ እምነት ለቼልሲ የዘንድሮው ዘመን ጥሩ መሆን አንቶኒዮ ኮንቴ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። እርሱም በአሰልጣኙ ስር መሆኑ የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ እንደረዳው ይናገራል። «በጨዋታዎች ላይ ዕድል አግኝቻለሁ። ሁሉም የቡድኑ አባላት ጥሩ ብቃት ላይ ይገኛሉ። ባገኘሁት አጋጣሚ ጎሎችን ለማስቆጠር ጥረት አደርጋለሁ። ይሄ ደግሞ ለእኔም ሆነ ለቡድኔ መልካም ነው። በራሴና በቡድኑ የዘንድሮ አቋም ምቾት ተሰምቶኛል። ዋንጫውንም እናነሳለን» በማለት በሙሉ የራስ መተማመን ተናግሯል።

አሁን ቼልሲ ሊጉን በ60 ነጥብ ሲመራ ተከታዩ ማንችስተር ሲቲ 52 ነጥብ አለው። ቶተንሀም እና አርሰናል በእኩል 50 ነጥብ በግብ ተበላልጠው 3ተኛ እና 4ተኛ ናቸው። ነገ ቼልሲ  ከስዋንሴ ሲቲ ጋር ሲገናኝ ፤ ቶተናም ከስቶክ ሲቲ ዕሁድ ዕለት ይጫወታሉ። ማንችስተር ሲቲ እና ማንችስተር ዩናይትድ የሚያደርጉት ጨዋታ ቀኑ በውል ባይታወቅም  ለሌላ ጊዜ ተዘዋውሯል። በተመሳሳይ አርሰናል ከሳውዝ ሀምፕተን የሚያደርጉት ጨዋታም ተዘዋውሯል።

ዳግም ከበደ

Published in ስፖርት

ኢትዮጵያ እና የቼስ ስፖርት የረጅም ዓመት ቁርኝት እንዳላቸው ይነገራል፡፡ ቼስ ስፖርት ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት «ሰንጠረዥ» በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ ውስጥ ይዘወተር እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የቼስ ስፖርት አካላዊ በሆነው እንቅስቃሴና ውድድር ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ጥንካሬ የሚሰጥ ሁለንተናዊ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑም  ስፖርቱን  በሚያዘወትሩ ሰዎች ተወዳጅ አድርጎታል፡፡

  ኢትዮጵያ በላልይበላ እና የአክሱም ሀውልት ቅርሶቿ እንደምትታወቀው ሁሉ በቼስ ስፖርትም ቀዳሚ ሀገር መሆኗን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ የቼስ ስፖርት አጀማመርን በተመለከተ በእንግሊዝ ሀገር በተጻፈው ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያ ባትጠቀስም ሪቻርድ ፓንክረስት በጻፉት የቼስ ስፖርት ታሪክ ውስጥ የቼስ ስፖርት ቀድሞ በተጀመረባቸውና ጨዋታው ከሚዘወተርባቸው ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን  አመልክተዋል፡፡ ሌሎችም የጥናት ውጤቶች ይህንኑ ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡

   ስፖርቱ በሀገሪቱ ረጅም ታሪክ ያለውን ያህል በሚፈለገው ደረጃ አለማደጉን በአንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ይነገራል፡፡ ትኩረት አጥቶ የነበረውና በደካማ ደረጃ እንደሆነ የተነገረለትን የቼስ ስፖርት ጨዋታ ወደተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  የለውጥ እንቅስቃሴዎች መታየት ጀምረዋል፡፡ በሀገሪቷ የቼስ ስፖርት ጨዋታ እንዲስፋፋና እንዲያድግ ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ ፌዴሬሽኑ ስፖርቱን ለማሳደግ የአሰልጣኝነት እና የዳኝነት ስልጠናዎችን በመስጠት ሙያዊ ብቃት ላይ የመጀመሪያውን ትኩረት አድርጓል፡፡

   ፌዴሬሽኑ ከክልሎችና ከአዲስ አበባ ከተማ ለተውጣጡ ከ20 በላይ ለሆኑ ባለሙያዎች የዳኝነት ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ከተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተውጣጡ የስፖርት ሳይንስ መምህራን ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ስልጠናው ምሁራንን ማዕከል ያደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡

      በዚሁ መሠረትም ከ30 የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ 54 የስፖርት ሳይንስ መምህራን አዲስ አበባ በሚገኘው ፌዴራል ቴክኒክ እና ሙያ ኢኒስቲትዩት ከየካቲት 6 ቀን 2009ዓ.ም ጀምሮ ስልጠናውን  እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ስልጠናውን በመውሰድ ላይ ከሚገኙት ሠልጣኞች መካከልም  ሴት መምህራን እንደሚገኙበት ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

       ስልጠናውን ከሚሰጡት መካከል ዋና አሰልጣኝ የሆኑት የኦሮሚያ ክልል ቼስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ አባልና በግላቸው በቼስ ስፖርት ላይ በርካታ ምርምሮችን እያደረጉ የሚገኙት ኢንስትራክተር ቶፊቅ በርሄ እንዳስረዱት ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በቼስ ስፖርት ውጤታማ አልነበረችም፣አሁን ግን ስፖርቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት አግኝቷል፡፡ ጠንካራ ሥራ አስፈጻሚዎችና ጠንካራ ኦፊሰር መመደቡ ስፖርቱ ትኩረት ማግኘቱን ያሳያል፡፡ የቼስ ስፖርት እንዲዘወተር እና በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚደረጉት ጥረቶች ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡«የቼስ ስፖርት ወደባለቤቶቹ ምሁራን ተመልሷል» ኢንስትራክተር ቶፊቅ የስፖርት ምሁራን የቼስ ስፖርትን መጀመራቸው ከስፖርታዊ ውድድሩ በተጓዳኝ ሀገሪቱ በርካታ ተመራማሪዎችን የማፍራት አቅም እንዲኖራት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ኢትዮጵያ በቼስ ስፖርት ከዓለም 125ኛ ደረጃ ላይ ትገኝ እንደነበር የተናገሩት ኢንስትራክተር ቶፊቅ በአሁኑ ጊዜ ግን በተሰጠው ትኩረት የተሻለ ዕድገት እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

   «ቼስ ስፖርት ከወድድር ባለፈ ለሀገሪቱ ዕድገት ቁልፍ  በሆኑት ትምህርት ተቋማት ውስጥ ከተዘወተረ  በርካታ ተመራማሪዎችን የማፍራት አቅም ይፈጥር ላታል፡፡» ያሉት አሰልጣኙ ቼስ ስፖርትን በትምህርት ዘርፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጠቀም ቀዳሚ የሆነችው አርመኒያ አስር ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ከ22ሺህ በላይ ተመራማሪዎችን ማፍራት መቻሏን ለአብነት አንስተዋል፡፡

       ኢንስትራክተር ቶፊቅ አክለውም ቼስ ስፖርትን ለመጫወት ሁሉንም የሚያሳትፍ ገደብ የሌለው መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይ ደግሞ ስፖርቱን ለማስፋፋት ማነቆ የሆነውን የስፖርቱን ቁሳቁስ በሀገር ውስጥ የማምረት ሥራዎች እንዲጠናከሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ «ይህንን ስልጠና ለመስጠት ሁለት ወር ተዘጋጅቼያለሁ፡፡ ሰልጣኞቹ የስፖርት ሳይንስ ምሁራን መሆናቸው ሃሳቡን በቀላሉ እንዲረዱት አስችሏቸዋል፡፡ በስልጠናው ላይ ከመጀመሪያ ድግሪ እስከ ፒኤችዲ የትምህርት ደረጃ ያላቸው መምህራን ተሳትፈዋል፡፡» በማለት አሰልጣኙ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

    ኢትዮጵያ በቅርቡ የዞን 4 ነጥብ 2 የቼስ ውድድርን በጅማ ከተማ ለማካሄድ ኃላፊነት መውሰዷ ለስፖርቱ የሰጠችውን ትኩረት እንደሚያሳይ የጠቆሙት አሰልጣኙ፣ ለሀገሪቱ የልማት ህዳሴ እውን መሆን ከፍተኛውን ድርሻ የሚወጡት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሁራን ቼስ ስፖርትን በማስፋፋትም በኩል ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ስልጠናውን በመውሰድ ላይ የሚገኙት ምሁራን ወደየመጡበት ትምህርት ተቋማት ሲመለሱ ክለቦችን ከማቋቋም ጀምሮ ቼስን ለማስፋፋት ጥረት እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

    «ቼስ ተጫዋች በባህሪው ለሚያጋጥሙት ችግሮች ፈጣን መፍትሔ የመስጠት አቅም ያለው ነው፡፡ ቼስ ከአካል ንክኪ ይልቅ በአዕምሮ ንክኪ ላይ የተመሠረተ በሳል አስተሳሰብን የሚጠይቅ ስፖርት ነው» ያሉት ኢንስትራክተር ቶፊቅ ምሁራኑ ወደ ዩኒቨርሲቲያቸው ሲመለሱ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ችግር ፈቺ ትውልድ በማፍራት በኩል ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

       የስልጠናው አስተባባሪና ሰልጣኝ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር ሥራ አስፈጻሚ አባልና ዋና ፀሐፊ አቶ መስፍን ወንድወሰን በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል «የኢትዮጵያ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር» በሚል ስያሜ ሲጠራ እንደነበርና ከዚህ ዓመት ጀምሮ ደግሞ «የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር» ተብሎ እንደሚጠራ ገልጸዋል፡፡ ማህበሩ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚካሄዱ  ስፖርቶችን በማስፋፋት ሥራዎች ድጋፍና ክትትል ያደርጋል፡፡ ማህበሩ ሥልጠናዎችንም ይሰጣል፡፡

  «በየትምህርት ተቋማቱ ምርምሮችን መሥራት እና በተለይ አዳዲስ ስፖርቶችን ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የማህበሩ ዓላማ እና ተግባር ነው፡፡» ያሉት ዋና ፀሐፊው አቶ መስፍን ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በሚሳተፉበት ዓመታዊ የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ደግሞ አዳዲስ የስፖርት ዓይነቶች የሚተዋወቁበት ዕድል እየተፈጠረ መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

   ዋና ጸሐፊው እንዳሉት ቼስ ስፖርት በትምህርት ተቋማት ሳይዘወተር የቆየ ስፖርት ነው፡፡ አሁን እየተሰጠ ባለው ስልጠና ችግሩ እንደሚቀረፍ እምነት ተይዟል፡፡ ሰልጣኞቹ ከስልጠና በኋላ ወደየመጡበት ትምህርት ተቋማት ሲመለሱ ተተኪ ተጫዋቾችን ከማፍራት ባሻገር የታዳጊ ፕሮጀክት ጣቢያዎችን በመደገፍ ቼስን ለማስፋፋት በርትተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

       በስልጠናው የተሳተፉትን የትምህርት ተቋማት አስመልክተው አቶ መስፍን እንደገለጹልን በስልጠናው እንዲሳተፉ በደብዳቤ ለ38 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጥሪ ቢደረግም ከመካከላቸው  አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች አልተሳተፉም፡፡ ማህበሩ በየዓመቱ በሚያካሂደው የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ቼስን ጨምሮ በ14 የስፖርት ዓይነቶች ውድድሮች እንደሚካሄዱም ገልጸዋል፡፡ ማህበሩ ስልጠናው ከተጠናቀቀ በኋላ ሰልጣኞቹ በስልጠናው ያገኙትን እውቀት በተግባር ማዋላቸውንም ከትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

        «ከአሁን በፊት ቼስ ተጫውቼ አላውቅም፡፡ ስልጠናውን ስወስድ ግን ቼስ አዕምሮን የማስፋት እና የማሰብ አቅምን የሚያሳድግ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡» ያሉት ደግሞ በስልጠናው ላይ አክሱም ዩኒቨርሲቲን በመወከል እየተሳተፉ የሚገኙት አቶ ለምለም ወልደጊዮርጊስ የአንደኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠና በቀጣይ በሌሎች ስልጠናዎች ከታገዘ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

       አቶ ለምለም አክለውም በዚህ ስልጠና ላይ ለመሳተፍ በፍቃደኝነት መምጣታቸውን ገልጸው፣ በስልጠናው ያገኙትን እውቀት ለተቋሙ ተማሪዎች፣ ደጋፊ ሠራተኞች እና መምህራን እንደሚያስተላልፉ አመልክተዋል፡፡ በሀገር አቀፉ የዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌስቲቫል ላይ ዩኒቨርሲቲያቸው ጠንካራ የሆነ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀርብ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

        የወሎ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ መምህርቷ ቅድስት ቢያድግልኝም በሰጠችው አስተያየት ቀደም ሲል ስለ ቼስ ስፖርት እውቀቱ አልነበራትም፡፡ ከስልጠናው ብዙ እውቀት እንዳገኘችና ከዚህ በኋላ ለቼስ ስፖርት ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ ገልጻለች፡፡ ስፖርቱ ለተለያየ ችግር ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግራለች፡፡

     የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን የስፖርቱ ባለቤት የሆኑት ምሁራን በትምህርት ተቋማቸው ውስጥ እንዲያዘወትሩት እየሰጠ ያለው ስልጠና እስከ ነገ ድረስ እንደሚቀጥል ከወጣው መርሐግብር ለመረዳት ተችሏል፡፡ ፌዴሬሽኑ ከዚህ ስልጠና ባሻገር ለትምህርት ተቋማቱ የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግም ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡  

ታምራት አበራ

Published in ስፖርት

አቶ ሰለሞን አንባቸው

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት ችግር ዛሬም አልተቀረፈም ። በተለይ ከሁለት ዓመት በፊት በስራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት በሰራተኛው ዘንድ ያደርስ የነበረው መጉላላትና መጨናነቅ አይዘነጋም።መንግስት እጥረቱ  በሰራተኞቹ ላይ ያሳደረውን ጫና ለመቅረፍ ያስችል ዘንድ  በስራ መግቢያ እና መውጪያ ሰዓት የሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ  ማድረጉም እንዲሁ የሚረሳ አይደለም።

     ይሄን የትራንስፖርት አገልግሎት  መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል በሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ ቁጥር 298/2006 የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋቋም አድርጓል::

      ድርጅቱ የተቋቋመበትን ዓላማ በማስፈፀም ረገድ ለፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎትን በተገቢው መልኩ ተደራሽ ለማድረግ በዕቅድ የያዘውን 410 አውቶብሶች በመረከብ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።ድርጅቱ አሁን እየሰጠ ባለው የሰርቪስ ትራንስፖርት አገልገሎት በዕቅድ የተያዘውን ተደራሽነት ከግቡ ማድረስ የተቻለ ሲሆን እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ ድርጅቱ በቀን በአማካይ 364 አውቶብሶችን በማሰማራት በቀን  በአማካይ  68,500 በላይ  የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞችን በማጓጓዝ ላይ ይገኛል። ድርጅቱ መስመር ሲዘረጋ ታሳቢ ያደረጋቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ነዋሪዎች ያለመግባታቸው እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ለተዘረጉት መስመሮች የተመደቡት አውቶብሶች የሰርቪስ ትራንስፖርት  አገልግሎት  በበቂ ሁኔታ እየሰጡ በመሆናቸው 46 አውቶብሶችን በስራ መግብያና መውጫ ሰዓት ለህብረተሰቡ የታክሲ አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ ተችሏል፡፡

     ድርጅቱ የአገልግሎቱን ተደራሽነት  በማሳደግ ረገድ መነሻ መስመሮችን ከ 27 ወደ 44 እንዲሁም የመዳረሻ መስመሮችን ከ11 ወደ 16 ማድረስ ችሏል፡፡ለፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኛው ከሚሰጠው የሰርቪስ የትራንስፖርት አገልግሎት ባሻገር ከስራ ሰዓት መግቢያ እና መውጫ ሰዓት ውጪ 156 አውቶብሶችን እንዲሁም በሙሉ ቀን የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ 46 አውቶብሶችን በማሰማራት በቀን በአማካኝ ለ 36,000 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

    ድርጅቱ በ2009 በጀት አመት  በመጀመሪያው ግማሽ አመት በዝግጅት እና በትግበራ ምዕራፍ የተከናወኑ  ተግባራትን  አስመልክቶ በፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የኮሚኒኬሽን ኃላፊአቶ ሰለሞን አንባቸውን  አነጋግረናል፦

    እንደ ኃላፊው ገለፃ የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ለፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኛው በሚሰጠው የሰርቪስና ለከተማው ህዝብ በሚያከናውነው የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት የተሻለ አፈፃፀም እያስመዘገበ ይገኛል።

    የድርጅቱ የ2009 በጀት አመት የግማሽ አመት የስራ አፈፃፀም ሲታይም በስራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት 390 አውቶብሶችን በግማሽ አመት ውስጥ ለማሰማራት አቅዶ ቢነሳም 364 አውቶብሶችን በመመደብ የዕቅዱን 93 ፐርሰንት ማሳካት ችሏል።ከላይ በዕቅድ ባስቀመጣቸው አውቶብሶችም 10 ሺህ ሰራተኞችን በደርሶ መልስ አገልግሎት ለመስጠት አቅዶ የነበረ ሲሆን ወደ ስራ ባሰማራቸው አውቶብሶች ከስምንት ሺህ በላይ ሰራተኞችን በማጓጓዝ የዕቅዱን 86 ፐርሰንት ማሳካቱን አብራርቷል፡፡ይህም ካለፈው አመት አመታዊ የስራ  አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ትግበራን ያሳየ ሲሆን፤ ተቋሙ በ2008 ዓ.ም የስራ ዘመን አመታዊ ዕቅድ ክንውን 390 አውቶብሶችን ወደ ሥራ ለማስገባት አቅዶ በ337 አውቶብሶች 12‚551‚143 ሰራተኞችን በድግግሞሽ በማጓጓዝ የዕቅዱን 67.4 ፐርሰንት አሳክቶ እንደ ነበር አቶ ሰለሞን አስታውሰዋል።

    እንደ አቶ ሰለሞን አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የተጠቃሚ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የዳሰሳ ጥናት በማከናወን አምስት አቅጣጫዎች ያሉት ሁለት የፐብሊክ ሰርቪስ የመነሻ መስመሮች በመክፈት የተገልጋዮችን ፍላጎት ማርካት ተችሏል።ይህም ድርጅቱ ለሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመበትን አላማ ለማሳካት ያለውን ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ያሳየም እንደሆነም ነው የሚያሰምሩበት።

    በሌላም በኩል የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልገሎትን የሚጠቀሙ የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን የኮሚኒኬሽን ኃላፊው ገልፀዋል።በተያዘው የግማሽ አመት የስራ አፈፃፀምም 11‚000 ሴት 13‚564 ወንድ ሰራተኞች የአገልግሎት መጠቀሚያ መታወቂያ መውሰዳቸውንም ተናግረዋል። ይህ በስድስት ወራት አፈፃፀም የታየው የተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመር ድርጅቱ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት የሚያመለክት መሆኑንም  ጠቁሟል፡፡ 

    አቶ ሰለሞን አክለውም እንደተናገሩት ተቋሙ ከሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች ባሻገር ለከተማው ህዝብ በተመጣጣኝ ዋጋ የታክሲ አገልግሎትም ከተቋቋመ አንስቶ እየሰጠ ይገኛል።በመሆኑም በ2009ዓ.ም የግማሽ አመት የስራ አፈፃፀምም በ166 አውቶብሶች ዘወትር በሥራ ቀናት እንዲሁም ቅዳሜ ግማሽ ቀን ጨምሮ በሰጠው አገልግሎት ከዕቅድ በላይ 106 ፐርሰንት ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ።በተጨማሪም በዕቅድ በተያዙ አውቶብሶች በቀን ከሶስት ሺህ በላይ የከተማውን ህብረተሰብ ለማጓጓዝ ታቅዶ፤ከአራት ሺህ በላይ ተሳፋሪዎች አገልግሎት በመስጠት የዕቅዱን 134 ፐርሰንት አሳክቷል።ይህም ካለፈው አመት አመታዊ የስራ ክንውን ሪፖርት ጋር ሲነፃፀር የ101 ፐርሰንት ዕድገት አሳይቷል።

    በተጨማሪም ፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በያዘው 2009ዓ.ም በጀት አመት ግማሽ አመት በሰጣቸው የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞችና የኮንትራት እንዲሁም የሊዝ ትራንሰፖርት አገልግሎት የተሻለ ገቢ ማስመዝገቡንም የኮሚኒኬሽን ሀላፊው ገልፀውልናል።

     አክለውም እንደገለፁት በዚሁ መሰረት ድርጅቱ ለፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች በሚሰጥ የትራንስፖርት አገልገሎት 238‚572‚174 ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ ነበር።ከፌዴራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች የዕቅዱን 100 ፐርሰንት ገቢ ማስግኘት ተችሏል። ይህም ድርጅቱ በ2008 አመታዊ ገቢው በዚሁ የአገልገሎት ዘርፍ 114,733,642.00ብር ገቢ ማስግኘት ችሎ የነበር ሲሆን፤ ይህም ከ2009 የስድስት ወር የስራ አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር በስድስት ወር አፈፃፀሙ የተሻለ እንደሆነ አብራርተዋል።

    በሌላ በኩልም በተቋሙ ለከተማው ማህበረሰብ በሚሰጠው የታክሲ አገልገሎት በዚሁ በስድስት ወር 8‚147‚310 ብር ገቢ ለማስግኘት ታስቦ፤  9‚735‚332.00 ገቢ በማስግኘት የዕቅዱን 119 ፐርሰንት ማሳካቱን አቶ ሰለሞን ገልፀው፤አክለውም እንደገለፁትም  በዚህ የታክሲ አገልግሎት የተገኘው ገቢ በ2008ዓ.ም ከተገኘው አመታዊ ገቢ ብር 13,412,985 ጋር ሲወዳደርም የግማሽ አመቱ የስራ አፈፃፀም  ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል።

    የኮንትራት ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው ይኸው ድርጅት ለተለያዩ ድርጅቶች አገልግሎት በመስጠት 3‚665‚587.00 ገቢ በማስግኘት በዕቅድ ተይዞ የነበረ ሲሆን፤ በትጋት በመስራት 1‚200‚000 ብር በላይ በማከናወን የዕቅዱን 305 ፐርሰንት ተግባራዊ መደረጉን ጠቁሟል።ባለፈው አመትም ድርጅቱ በበጀት አመቱ ውስጥ ለተለያዩ ድርጅቶች የኮንትራት አገልግሎት በመስጠት በድምሩ ብር 2,105,036.00 ገቢ ያስገኘ ሲሆን፤ ይህም በ2009ዓ.ም የግማሽ አመት የስራ አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር በሁለቱም የስራ ዘመን በኮንትራት ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፉ የተሻለ ሥራ ማከናውኑን ያመላክታል» ብለዋል።ይህን የተሻለ ገቢ ማግኘት የተቻለው ተቋሙ የሚሰጠውን አገልገሎት በሚዲያ የማስተዋወቅ ሥራ መሰራት በመቻሉም እንደሆነ ጠቁመዋል።

    አቶ ሰለሞን እንደገለፁት ፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል አንዱ በሆነው የሊዝ ትራንስፖርት አገልግሎትም መልካም የሚባል አፈፃፀም አስመዝግቧል። በዚሁ የአገልግሎት ዘርፍ 4‚633‚200.00 ገቢ ለማግኘት አቅዶ 4‚018‚809 ብር ገቢ በማስገኘት 87 ፐርሰንት የዕቅድ ክንውን አስመዝግቧል።

    ኃላፊው በመጨረሻ ምንም እንኳ ድርጅቱ አገልግሎቱን አዳዲስ በተከፈቱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለመስጠት ዕቅድ ነድፎ ቢንቀሳቀስም ነዋሪዎቹ ባለመግባታቸው ፈተና ቢሆንበትም በ2009 ዓ.ም ባከናወነው የስድስት ወራት ስራ አፈፃፀም  ውጤታማ ሆኗል፡፡  በተጨማሪም በ2009ዓ.ም በግማሽ አመቱ የስራ አፈፃፀም የተገኘው ገቢ በ2008ዓ.ም ከተገኘው አመታዊ ገቢ ጋር ሲነፃፀር የተሻለ እድገት ማሳየት ችሏል።ይህም ውጤት ሊመዘገብ የቻለው በየስራ ዘርፉ የተሻለና ክትትል ያለው የስራ ክንውን በመካሄዱ ነው።

ወይንሸት ካሳ

Published in ኢኮኖሚ

በጨርቃ ጨርቅ ስፌት የተደራጁት የጰራቅሊጦስ ድርጅት አባላት በከፊል

ያደጉ አገራት መንግስታት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ለዜጎቻቸው ወይም በስደት በምድራቸው ለተጠለለ ህጋዊ የውጭ ዜጋ ራሱን ችሎ እንዲቆም ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ቢኖር ክፍት የሆነ የስራ በር ማመላከት ነው። ይህም ማለት ዜጋው ስራ ሳይንቅ፣ ሳያማርጥ፣ ሙያ ያለው በሙያው ትምህርት ያለው በትምህርቱ ሌላው ደግሞ አቅሙ በፈቀደው የስራ መስክ ተሰማርቶ በጉልበቱ እንዲሰራና ራሱን እንዲለውጥ ማመቻቸት ነው።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስትም ዜጎች ስራ ሳይንቁ ማንኛውንም ስራ እንዲሰሩና  ውጤታማ እንዲሆኑ በተለያዩ ዘርፎች ድጋፎችን እያደረገ ሲሆን፤ እነዚህን ከቁብ ባለመቁጠርና ስራ በማማረጥ በርካቶች ስራ አጥ /ቦዘኔ/ እንደሆኑ ሁሉ፤ ስራን ሳይንቁና ሳያማርጡ ከአንድ ሙያ ወደ ሌላው በመዘዋወር ብሎም አዋጭውን ይዞ በመቀጠል ውጤታማ መሆናቸውን የሚገልጹትም በርካቶች ናቸው። በተለይም በጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች ዘርፍ ተሰማርተው ህይወታቸውን መቀየር የቻሉ በርካቶች ናቸው። ይሁን እንጂ በጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ተሰማርተው ጥራታቸውን የጠበቁ ግብዓቶችን ማግኘት ባለመቻል ተፈላጊ፣ ከውጭ ጋር ተወዳዳሪ የሆኑና ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችን ለማምረት መቸገራቸውን፤ ይህም በገበያቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያስከተለ እንደሚገኝ በዘርፉ የተሰማሩ ይገልጻሉ።

ፋኖስ ፀጋዬ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመካኒካል ኢንጂነሪንግ በዲግሪ ተመርቃ በአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በሽያጭ ሰራተኝነት መቀጠሯንና ለበርካታ አመታትም በድርጅቱ መስራቷን ትናገራለች፤ ሆኖም በድርጅቱ በሽያጭ ሰራተኝነት በሰራችባቸው ጊዜያቶች ልብስ መስፋት፣ የልብስ ዲዛይን ማውጣትና ሌሎችን ሙያዎች ከለመደች በኋላ ከቅጥር በመውጣት በ2005ዓ.ም በሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር በጥቃቅንና አነስተኛ እንደተደራጀች ትገልጻለች።

“መካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት እንደመማሬ በጨርቃ ጨርቅ ስራ ህይወቴን እቀይራለሁ ብዬ አንድም ቀን አስቤ አላውቅም ነበር። ሆኖም በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ተቀጥሬ ስሰራ በጨበጥኩት ሙያና ከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጀው የስራ ቦታ፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎትና ሙያዊ ድጋፎች በማግኘቴ  ጰራቅሊጦስ የአልባሳት ማምረቻ ድርጅት መስራች አባል በመሆን ህይወቴን መቀየር ችያለሁ” ትላለች። 

ወጣት ፋኖስ እንደምትለው፤ በሻሸመኔ ከተማ የሚገኘው ጰራቅሊጦስ የማምረቻ ድርጅት የተለያዩ  ቲሸርት፣ ፓካውት፣ ጋዎንና የህጻናት አልባሳት የሚያመርት ሲሆን፤  ለ25 ወጣቶች የስራ እድል ፈጥሯል። ድርጅቱ ስራውን በ20ሺ ብር ካፒታል መነሻነት የጀመረ ሲሆን፤ አሁኑ ወቅት የድርጅቱ ካፒታል 260 ሺ ብር ደርሷል። እንዲሁም በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የዲፕሎማ ትምህርት ያጠናቀቁ፣ ከ10 እና 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ያጠናቀቁና ጀምረው ያቋረጡ የከተማዋ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል። ይሁን እንጂ ጥራታቸውን የጠበቁ፣ ጥሩ ዋጋ ሊያወጡና የውጭ አገር ምርትን ሊተኩ የሚችሉ አልባሳትን ለማምረት ጥራት ያለው ግብዓት አስፈላጊ በመሆኑና ደረጃውን የጠበቀ ምርት በቀላሉ ማግኘት ባለመቻሉ በስፋት እንዳንሰራ፤ ይህም በገበያ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከመፍጠሩም ባሻገር ምርቱ በሁሉም ቦታ ተደራሽ እንዳይሆንና ተፈላጊነቱ እንዲያንስ ተጽዕኖ ማስከተሉን ይናገራሉ፡፡  

“ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች በጥራት ደረጃ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ በሁሉም አይነት ጨርቆች ምርቶችን ማቅረብ አለመቻላቸውና  ህብረተሰቡ ለአገር ውስጥ ምርት ከሚሰጠው ግምት አነስተኛ መሆን ጋር ተዳምሮ የሚመረቱ ምርቶች ገበያ ላይ ተግዳሮትን ይፈጥራል” የምትለው ወጣት ፋኖስ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምርቱ እየተለመደና እየተሻሻለ መምጣቱ የተሻለ ገበያ እንዲገኝ እድል ቢከፍትም፤ ለአልባሳት ግብዓት የሚውሉ ጨርቃ ጨርቆችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች የተሻለ ጥራት ያለው ምርት ቢያመርቱ እኛ የምናዘጋጃቸው ምርቶች በጥራት ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን ይችላሉ ባይ ነች።

በሂሳብ ትምህርት በዲፕሎማ ተመርቃ በተማረችበት ዘርፍ ስራ ባለማግኘቷ በድርጅቱ ተቀጥራ ያገኘኋት ወይዘሮ ከድጃ ጀማል፤ የአንድ ሙያ ባለቤት ስለሆንኩ ግዴታ በተማርኩበት ልስራ ማለት የለብኝም፤ በእርግጥ በሂሳብ ስራ በዲፕሎማ ተመርቄያለሁ፤ ሆኖም በተማርኩበት ዘርፍ ስራ ማግኘት ባለመቻሌ ስራ ሳላማርጥ ወደ ሙያው ገብቻለሁ። በጰራቅሊጦስ የአልባሳት ማምረቻ ድርጅት ተቀጥሬ በመስራቴ የልብስ ስፌት መኪና፣ ዲዛይን፣ ኦቨርሉክ መምታትና ሌሎችንም መማር ችያለሁ፤ ወደፊት የልብስ መኪና ማሽን በመግዛት የግል ስራዬን ለመስራት እያሰብኩ ነው ትላለች።

በድርጅቱ ተቀጥራ እየሰራች ያገኘኋት ወጣት ውቢት ግርማይ፤ ወደ ድርጅቱ የተቀጠረችው ምንም አይነት የልብስ ስፌት ሙያ ሳይኖራት 10ኛ ክፍል እንዳጠናቀቀች መሆኑንና አሁን ላይ የልብስ ስፌት ማሽን ስራ በደንብ መቻሏን ትገልጻለች። በቀጣይም ሙያውን በማሳደግ የተለያዩ ዲዛይን ያላቸውን አልባሳት መስራት ስትችልና አስፈላጊ ግብዓቶችን ስታሟላ የግሏን በመክፈት ለመስራት ማቀዷን ታስረዳለች።

በሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር የስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ደስታ ዋሪቱ፤ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ በከተማዋ በርካታ ወጣቶች ተደራጀተው የተለያዩ አልባሳትን እያመረቱ ሲሆን፤ መንግስት ያመቻቸላቸውን የመስሪያ ቦታ፣ የማሽነሪ አቅርቦት፣ የብድርና ሌሎች ግብዓቶችን  በመጠቀም ገበያውን ሰብረው በመግባት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። በመጀመሪያ አካባቢ የገበያ ችግር የነበረባቸው በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ የገበያ ማዕከል በሆኑ የከተማዋ አካባቢዎች መሸጫና ማከፋፈያ ሱቅ እንዲያገኙ በማድረግ ችግሩ እንዲፈታላቸው አድርጓል። በተጨማሪም ቅዳሜና እሁድ መሸጫ ቦታ እንዲዘጋጅላቸው በማድረግ ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ እንዲያወጡና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመደረጉ በከተማዋ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ጰራቅሊጦስ የአልባሳት ማምረቻ ድርጅት አንዱ መሆኑንም ይናገራሉ።

ድርጅቱ ስራውን ሲጀምር አነስተኛ ካፒታል፣ ውስን የሰው ሃይል የነበረው ሲሆን፤ አሁኑ ወቅት ካፒታሉ ማደጉንና ተሽከርካሪ በመግዛትም ወደ መሃልና አጎራባች ከተሞች በመንቀሳቀስ ምርቶቹን እያስተዋወቀና እየሸጠ እንደሚገኝም የሚገልጹት  አቶ ደስታ፤ ከቴክኒክና ሙያ እንዲሁም ከኮሌጆች ለተመረቁ ወጣቶች በድርጅቱ የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ያስረዳሉ።

በተሻለ ደረጃ ምርቶችን ለማምረት የሚያስችሉ ጥራታቸውን የተጠበቁ ጥሬ እቃዎች በሚፈለገው ሁኔታ ገበያው ላይ አለመገኘት በዘርፉ ላይ የጥራት ችግር እያስከተለ እንደሚገኝ የሚናገሩት አቶ ደስታ፤ በአገሪቱ የሚገኙና ለግብዓትነት የሚውሉ ጨርቃ ጨርቆችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች የምርቶቻቸውን ደረጃ ማሳደግና የተሻለ ግብዓት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። ምክንያቱም ጉዳዩ እየፈተነ ያለው ብትን ጨርቆችን ከአምራች ድርጅቶች ተቀብለው የተለያዩ አልባሳትን ማለትም ቲሸርት፣ ሹራብ፣ ጋዎን፣ ዩኒፎርም፣ የህጻናት ልብስ፣ ኮትና የመሳሰሉትን እያመረቱ የሚገኙ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የሚገኙ ድርጅቶችን ነው ይላሉ።

በከተማዋ በአገልግሎት፣ በማኑፋክቸሪንግ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች መኖራቸውንና ለሁሉም አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማሟላት ከተማ አስተዳደሩ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ የሚገልጹት አቶ ደስታ፤ መንግስት በአገር አቀፍ ደረጃ ለወጣቱ የመደበውን 10 ቢሊዮን ብር እንደ ከተማ አስተዳደር በተገቢው ሁኔታ በጀቱን መቶ በመቶ ለመጠቀምና በከተማዋ ያሉ ስራ ፈላጊዎችን በማደራጀት የበለጠ ለመስራት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ይገልጻሉ።

አቶ ደስታ እንዳሉት፤ በከተማዋ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተሰማሩ አንቀሳቃሾችን ወደ መካከለኛ ደረጃ ለማሸጋገር ድርጅቶቹ ያሉበት ደረጃና ያላቸው ጠቅላላ ካፒታል ሂሳብ ስራ እየተሰራ ሲሆን፤ አሟልተው የሚገኙት ወደ መካከለኛ ደረጃ የሚሸጋገሩበት ሁኔታ እየተመቻቸላቸው ነው። እንዲሁም ድርጅቶቹ የውጭ ምርቶችን የሚተካ ጥራት ያለው ምርት እንዲያመርቱ፣ አትራፊ እንዲሆኑና በቂ ገበያ እንዲያገኙ የበለጠ መስራት ያስፈልጋል።

በዑመር እንድሪስ

Published in ኢኮኖሚ

ሌተናል ጀኔራል ማይክል ቶማስ ፍሌን

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የነበሩት ሌተናል ጀኔራል ማይክል ፍሌን ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ ለወትሮውም በአወዛጋቢነታቸው የሚታወቁትን ዶናልድ ትራምፕንና አስተዳደራቸውን ለበለጠ ትችትና ተቃውሞ እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡ ሌተናል ጀኔራል ማይክል ፍሌን ከኃላፊነታቸው እንዲለቁ ያስገደዳቸው ጉዳይ አማካሪው ዶናልድ ትራምፕ የፕሬዚዳንትነቱን ስልጣን ከባራክ ኦባማ ከመረከባቸው በፊት በአሜሪካ የሩስያ አምባሳደር ከሆኑት ሰርጌ ኪስላክ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ባራክ ኦባማ ስልጣናቸውን ከማስረከባቸው ከጥቂት ቀናት በፊት በሩስያ ላይ የጣሉት ማዕቀብ ስለሚቃለልበት ብሎም ስለሚነሳበት አግባብ ተነጋግረዋል በሚል ወቀሳ ነው፡፡

አማካሪው ከሩስያ አምባሳደር ጋር በስልክ ብወያይም ስለማዕቀቡ ምንም የተነጋገርነው ነገር የለም በማለት በተደጋጋሚ የቀረበባቸውን ወቀሳ አስተባብለዋል፡፡ ለምክትል ፕሬዚዳንቱ ማይክ ፔንስ ጨምሮ ለሌሎች ከፍተኛ የዋይት ሀውስ ባለስልጣናትም የቀረበባቸው ትችትና ወቀሳ ከእውነት የራቀ መሆኑን አስረድተው ነበር፡፡ ማይክ ፔንስም አማካሪው ከአምባሳደር ሰርጌ ኪስላክ ጋር ባደረጉት ውይይት ስለማዕቀቡ የተነጋገሩት ነገር እንደሌለ ለሲ.ቢ.ኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአገሪቱ ታላላቅ የመገናኛ ብዙኃን የአማካሪውን ማስተባበያ የሚያከሽፉ መረጃዎችን ይፋ ማድረጋቸውንና አማካሪውም ከአምባሳደሩ ጋር ስለነበራቸው ውይይት ለምክትል ፕሬዚዳንቱና ለሌሎች ባለስልጣናት የሰጡት መረጃ ያልተሟላና ያልተስተካከለ እንደነበር መናገራቸውን ተከትሎ ሌተናል ጀኔራል ማይክል ፍሌን ባለፈው ማክሰኞ ዕለት ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸው ሲሰማ ቀድሞውንም ቢሆን የዶናልድ ትራምፕን አስተዳደር ብቃት በጥርጣሬ በሚመለከቱት ወገኖች ዘንድ ይበልጥ ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል፡፡

አሁን የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የነበሩት ማይክል ፍሌን ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸው ሌሎች ጉዳዮችን እየጎተተ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካውያን የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን አስተዳደር በስጋትና በጥርጣሬ እንዲመለከቱት አድርጓል፡፡ አማካሪው ከስልጣን ቢለቁም ገና ምላሽ ያላገኙ በርካታ ጥያቄዎች ስለመኖራቸውም በሰፊው እየተነገረ ይገኛል፡፡ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማካሪያቸውን ከኃላፊነት ለማንሳት ለምን እስካሁን ዘገዩ? የሚለው ጥያቄ መልስ ከሚሹ ብዙ ጥያቄዎች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡

ዘ ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ በእትሙ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የነበሩት ሳሊ ያትስ ማይክል ፍሌን ከአምባሳደር ኪስላክ ጋር ባደረጉት ውይይት ስለማዕቀቡ መነጋገራቸውን የሚገልፅ መረጃ እንደተገኘ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት ማግስት ለዋይት ሀውስ ባለስልጣናት አሳውቀው እንደነበር የሚገልፅ ዘገባ ይፋ አድርጓል፡፡ ፕሬዚዳንቱም ይሁኑ ባለስልጣኖቻቸው ጉዳዩን ካወቁ አማካሪው ምክትል ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ሌሎች የስራ ኃላፊዎችን እስኪያሳስቱ ድረስ ለምን ዝም እንዳሉ እስካሁን ምላሽ አልተገኘም፡፡

የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ሾን ስፓይሰር ማክሰኞ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ማይክል ፍሌን ከአምባሳደሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ማዕቀቡን በተመለተ ስለመነጋገራቸው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከበዓለ ሲመታቸው አምስት ቀናት በኋላ እንዳወቁና ጉዳዩ እንዲጣራ (በተለይ የአገሪቱ ህግጋት ስለመጣሳቸው እንዲብራራ) ትዕዛዝ ሰጥተው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ቀናት እየጨመሩ ሲመጡ ፕሬዚዳንቱ በአማካሪያቸው ላይ ያላቸው እምነት እየተሸረሸረ በመምጣቱ ማይክል ፍሌን ከኃላፊነታቸው ሊለቁ ችለዋል  ብለው ተናግረዋል፡፡

 ሾን ስፓይሰር “ ቀናት” ብለው በንግራቸው የገለጿቸው ጊዜያት፣ ሌተናል ጀኔራል ማይክል ፍሌን ኢራን ለደህንነት ስጋት መሆኗን የተናገሩባቸው፣ ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ከጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ጋር በመሆን ስለ ሰሜን ኮርያ የሚሳይል ሙከራ የተወያዩባቸው፣ እንዲሁም  በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ውይይትና ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙባቸው ጊዜያት መሆናቸው ሲታወቅ የአማካሪው ስህተት በፕሬዚዳንቱ ምን ያህል ችላ ተብሎ እንደነበር ማሳያዎች ስለመሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡

የአማካሪውን መልቀቅ ተከትሎ ምርመራ ይካሄዳል ወይንስ ስልጣን መልቀቃቸው እንደ ማካካሻ ይታይላቸዋል? የሚለው ጉዳይ ሌላው ምላሽ ያላገኘ ጥያቄ ተደርጎ ተቆጥሯል፡፡ የዴሞክራቲክ ፓርቲ የኮንግረስ አባላት ከማይክል ፍሌን መልቀቅ በስተጀርባ ያሉ ጉዳዮች በዝርዝር እንዲጠኑ ጥሪ ለማቅረብ የቀደማቸው አልነበረም፡፡ ለአብነት ያህል ናንሲ ፔሎሲ፣ የአሜሪካ ህዝብ ሩስያ በፕሬዝደንት ትራምፕ ላይ ያላትን ግለሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነትና ጉዳዩ በብሔራዊ ደህንነታችን ላይ ያለውን አንደምታ የማወቅ መብት አለው በማለት አስቸኳይና ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ አሳስበዋል፡፡

ዴሞክራቶች ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩ በዝርዝር እንዲታይ ቢፈልጉም ሩስያ በ2016ቱ በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ ስለመግባቷ ለማጣራት የተያዘ ራሱን የቻለና በሴኔቱና በምክር ቤቱ የደህንነት ኮሚቴዎች የሚመራ ትልቅ ዕቅድ ስላለ ለጊዜው ፍላጎታቸው የሚሳካ አይመስልም፡፡ በተጨማሪም አዲስና ልዩ ኮሚቴ ይቋቋም የሚለውን ሃሳብ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላትም ተቃውመውታል፡፡ ይሁን እንጂ ልዩ ኮሚቴ ሳይቋቋም በጉዳዩ ላይ ምርመራ እንዲካሄድ ለቀረበው ሃሳብ ዴሞክራቶችና ብዙ ሪፐብሊካኖች ድጋፋቸውን ችረዋል፡፡ 

ሌሎች የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት በበኩላቸው የማይክል ፍሌን ከስልጣን መልቀቅ ሩስያ አሁንም ለአሜሪካ ደህንነት ትልቅ ስጋት እንደሆነች እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል፡፡ አንጋፋው ሴናተር ጆን ማኬይን፣ “የሌተናል ጀኔራል ማይክል ፍሌን ከስልጣን መልቀቅ የትራምፕ አስተዳደር ለቭላድሚር ፑቲኗ ሩስያ ያለው ዕይታ ላይ ጥያቄ ያስነሳል” ብለዋል፡፡    

ይሁን እንጂ አንዳንድ ሪፐብሊካን የኮንግረስ አባላት ደግሞ ጉዳዩን ከቁብ የቆጠሩት አይመስልም፡፡ የምክር ቤቱ የቁጥጥር ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ጀሰን ቻፌዝ፣ “የራሱ ጉዳይ” የሚል ዓይነት አንደምታ ያለው አስተያየት በመስጠት፣ ከሌተናል ጀኔራል ማይክል ፍሌንና ከአምባሳደር ሰርጌ ኪስላክ የስልክ ውይይት ይልቅ ሊቀ-መንበሩን አሁንም የሚያሳስባቸው የሂላሪ ክሊንተን የግል የኢ-ሜይል አድራሻቸውን ለመንግሥት ስራዎች የመጠቀማቸው ክስ ሳይጣራ መቅረቱ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ እ.አ.አ በ1799 የፀደቀውና የሎጋን ህግ (Logan Act) የሚባለው የፌደራል ድንጋጌ ተጥሷል ወይንስ አልተጣሰም? የሚካሄደውስ ምርመራ ይህንን ያጠቃልላል? የሚለው ሃሳብ ነው፡፡ ይህ ህግ ስልጣን የሌላቸው አሜሪካውያን ግለሰቦች በአገራቸው ጉዳይ ላይ ከውጭ መንግሥታት ጋር የመነጋገርም ይሁን የመደራደር መብት እንደሌላቸው ይደነግጋል፡፡ አማካሪው ጉዳዩን የፈፀሙት ኃላፊነት ከመያዛቸው በፊት በመሆኑ እንዲሁም የፖለቲካ ቅሌቶችን ለመሸፈን የተፈፀሙ ድርጊቶች በወንጀል ክስ ጥፋተኛ ሊያስብሉ እንደሚችሉ ደግሞ ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ታሪክ ስለታዩ ምርመራው በህጉ ላይ መጣስ መፈፀሙንና አለመፈፀሙን ማየት የሚያካትት ከሆነ ፕሬዚዳንት ትራምፕንና አስተዳደራቸውን የባሰ ጣጣ ውስጥ ሲከታቸው ታይቷል፡፡

የፕሬዚዳንቱ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ከስልጣን እንዲለቁ ያበቃቸውን ጉዳይ ቀድሞ መቆጣጠር አይቻልም ነበር ወይ? ሌላው ያልተመለሱ ተብለው ከተለዩት ጥያቄዎች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ የአሜሪካ የመከላከያ ደህንነት መስሪያ ቤት ዳይሬክተር ሆነው የሰሩት ሌተናል ጀኔራል ማይክል ፍሌን የሩስያ አምባሳደር  በሚያደርጓቸው የስልክ ንግግሮች ሁሉ በአሜሪካ መንግሥት ስለላ እንደሚደረግበት አያውቁም ብሎ መገመት ሞኝነት ነው፡፡ ታዲያ ማይክል ፍሌን ይህንን እያወቁ ኃላፊነት ከመረከባቸው አስቀድመው ስለማዕቀብ ማውራታቸው የሚያሳየው ያለባቸውን ማንአለብኝነት አልያም ግዴለሽነት ነው በሚል አወዛጋቢ ሆኗል፡፡

ዶናልድ ትራምፕም ሆኑ ባለስልጣኖቻቸው ከጠቅላይ አቃቤ ህግ መስሪያ ቤት የደረሳቸውን መረጃ በጥልቀት በማጤን ፈጣን ምላሽ ቢሰጡ ኖሮ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ማይክ ፔንስ አማካሪው ከአምባሳደር ሰርጌ ኪስላክ ጋር ባደረጉት ውይይት ስለማዕቀቡ የተነጋገሩት ነገር እንደሌለ ለሲ.ቢ.ኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረው ህዝብ ባላሳሳቱ ነበር ተብለው እየተብጠለጠሉ ነው፡፡

ከኃላፊነት በለቀቁት ሌተናል ጀኔራል ማይክል ፍሌን ተተክተው የብሔራዊ ደህንነት አማካሪነቱን ስራ የሚመሩት ቀጣዩ ሰው ማን እንደሆኑ በብዙዎች ዘንድ በጉጉት እየተጠበቀ ይገኛል፡፡ ኃላፊነታቸውን የለቀቁት ማይክል ፍሌን ከምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ጀምሮ ለዶናልድ ትራምፕ በጣም ታማኝ ሰው ስለነበሩ እርሳቸውን የሚተካ ሌላ ታማኝ አማካሪ ለማግኘት ዶናልድ ትራምፕ ይቸገራሉ እየተባለም ነው፡፡ የማይክል ፍሌንን ከስልጣን መልቀቅ ተከትሎ ሌተናል ጀኔራል ኬዝ ኬሎግ የፕሬዚዳንቱ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ እንዲሆኑ በጊዜያዊነት ተሹመዋል፡፡ እ.አ.አ. በ2003 ከጦሩ በጡረታ የተሰናበቱት ሌተናል ጀኔራል ኬዝ ኬሎግ በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ዶናልድ ትራምፕን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች ላይ ሲያማክሯቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

የፕሬዚዳንቱ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ይሆናሉ ተብለው ሰፊ ግምት ከተሰጣቸው ግለሰቦች መካከል የአሜሪካ ደህንነት መስሪያ ቤት  የቀድሞ ዳይሬክተር ደቪድ ፒትሪየስ ዋነኛው ናቸው፡፡ ምስጢራዊ መረጃዎችን ለአንድ ጋዜጠኛ አሳልፈው ሰጥተዋል ተብለው ከሲ.አይ.ኤ የተሰናበቱት ፒትሪየስ፣ ይህ ታሪካቸው በዕጩነታቸው ላይ መጥፎ ጥላ ያጠላል ተብሏል፡፡ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ የቀድሞ ምክትል አዛዥ የነበሩት ሮበርት ሃርዋርድ ቦታውን ሊረከቡ ይችላሉ ተብለው ከታሰቡት ዕጩዎች መካከልም አንዱ ስለመሆናቸው እየተዘገበ ይገኛል፡፡

አወዛጋቢ የምርጫ ቅስቀሳቸውን አልፈው በአወዛጋቢ ሁኔታ የነጩን ቤት የፕሬዚዳንትነት መንበር ከተረከቡ ገና አንድ ወር እንኳን ያልሞላቸው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ጆን ትራምፕ፣ በአወዛጋቢ ውሳኔዎቻቸው እንዲሁም ባለስልጣኖቻቸው ታጅበው ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ማወዛገባቸውን ቀጥለ ውበታል፡፡               

   አንተነህ ቸሬ

Published in ዓለም አቀፍ

መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የመንግስት ሰራተኞች ግንባር ቀደም ሚና እንደሚጫወቱ እሙን ነው። የመልካም አስተዳደር እጦት በቅርቡ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ለተነሱ ሁከቶች ዋንኛ ምክንያት ነበር። መንግስት  ችግሮቹን ለመቅረፍ ከሚያ ደርጋቸው በርካታ ጥረቶች መካከል የመንግስት ሰራተኞች አገልግሎት አሰጣጥ የሚፈተሽበት አካሄድ እንዲመቻች አድርጓል።

ሰሞኑን በተለያዩ የክልልና የፌዴራል  የመንግስት ሰራተኞች አካላት የተሃድሶ መድረኮች በመካሄድ ላይ ናቸው። እነዚህ የተሃድሶ መድረኮች እንዲካሄዱ መንግስት ሁኔታዎችን ማመቻቸቱ እጅግ በጣም ጥሩ ይመስለኛል። የመንግስት ሰራተኞች ለህብረተሰቡ የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ለማሻሻል የሚያስችለው በመሆኑ በጥልቀት የመታደስ መድረኮች ለውጥ ያመጣሉ ብዬ አስባለሁ። አንዳንድ ሰዎች “በጥልቀት ተሃድሶ” የሚለውን አካሄድ ከኢህአዴግ ጋር ብቻ ሲያገናኙት ይታያሉ። ይሁንና ይህ አስተሳሰብ ትክክል አይደለም። የተሃድሶ ዋንኛ አላማ የመንግስት አገልግሎቶችን በማሻሻል መልካም አስተዳደርን በማስፈን አገራችን የጀመረችውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና  ልማት ማፋጠን ነው።

ለመልካም አስተዳደር  መጠናከርም ሆነ መድከም  የመንግስት (የበላይ አመራሩ) ሚና የማይተካ ቢሆንም  የመንግስት ሰራተኞች  ሚናም  በቀላሉ የሚታይ አይደለም። መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የላይኛው የመንግስት አካል  የትኛውንም ያህል ጥረት ቢያደርግ  የታችኛው ፈጻሚ አካልና  አገልግሎት ተቀባይ (ህብረተሰቡ)  ግዴታቸውንና መብታቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁ ማድረግ  ተገቢ ነው።  አሁን እነዚህን  የተሃድሶ መድረኮች በመጠቀም ሁሉም በየደረጃው በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ማለፍ  መልካም ነገር ነው።

የኢህአዴግ አመራርና አባላት ይታደሳሉ፤ የመንግስት ሃላፊና ፈጻሚ (የመንግስት ሰራተኞች) ይታደሳሉ፣ ህብረተሰቡ ይታደሳል። በእርግጥ የግምገማው ነጥቦች፣ ደረጃውና አካሄዱ ለየቅል ይሁን እንጂ   ሁሉም በየደረጃው በተሃድሶው ውስጥ ማለፍ ይጠበቅባቸዋል። መታደስ ማለት  “የመንግስት የስራ ሃላፊነት ለህዝብ አገልግሎት ማዋል” ማለት ነው። መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የመንግስት ሰራተኞች ለህዝብ  የሚሰጡትን አገልግሎት ማሻሻል የመጀመሪያ ተግባር ነው።  የመንግሥትን ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞች እና ዕቅዶች የሚያስፈጽመውና  የሚፈጽመው የመንግስት ሰራተኞች በመሆናቸው አገልግሎቶችን ለማሻሻል  መታደስ የግድ ይላቸዋል፡፡  ይታደሳሉ ሲባል በፖለቲካ አመለካከታቸው ወይም ወገንተኝነታቸው ሳይሆን  ስራን ብቻ ማዕከል ያደረገ ነው።

የመንግስት አሰራር ግልጽነትና ተጠያቂነት የነገሰበት እንዲሆን ህገመንግስቱ ይደነግጋል።  በመሆኑም እየተካሄደ ያለው  የተሃድሶ መድረኮች  የመንግስት ሰራተኞች ህዝብን ለማገልገል የገቡትን ቃል ለመፈጸም የሚያስችላቸውን አቅም የሚፈጥርበት መድረክ በመሆኑ በአግባቡ መካሄድ ይኖርበታል።  የመንግስት ሰራተኞች በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ በማለፍ ጠንካራ  የአገልጋይነት መንፈስ  መላበስ  የሚያስችላቸውን አቅም ስለሚያገኙ አገራችን የጀመረችውን  ፈጣን እድገት የሚያስ ቀጥሉበት አቅም ይፈጥርላቸዋል።

የመንግስት ሰራተኞች ህብረተሰባዊ አስተሳሰብን መላበስ ለአገልግሎት አሰጣጥ አስፈላጊ ናቸው። የታደሉት ለህዝባዊነት ሲሉ ህይወታቸውን ገብረዋል፤ አካላቸውን አጉድለዋል። ይህ ትውልድ ያን አይነት መስዋዕትነት አይጠበቅበትም። ይልቁንም ከዚህ ትውልድ የሚጠበቀው  በተሰማራበት መስክ የተጣለበትን አደራ  በአግባቡ መወጣት መቻል ነው። ለህብረተሰቡ የሚሰጠው አገልግሎት ሲሻሻል  የአገራችን ዕድገት ይፋጠናል በዚህም እኔም ተጠቃሚ እሆናለሁ የሚል አስተሳሰብ ሊያዳብር ይገባል።

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 12/1/ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት ባለው  መንገድ መከናወን አለበት በሚል በተደነገገው መሠረት የመንግስት ሰራተኞች ለዜጎች የሚሰጡት አገልግሎት ከአድልዎ የፀዳ በመርህ ላይ የተመሠረተ መሆን መቻል አለበት፡፡ በመሆኑም የመንግስት ሰራተኞች  የአገልግሎት መሻሻል ከህልውናቸው ጋር  የተያያዘ  መሆኑን  በመረዳት እንዚህን የተሃድሶ መድረኮች በአግባቡ መጠቀም ይኖርበታል።  ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ይባላል። እውነት ነው፤ የመንግስት ሰራተኞች መረዳት ያለባቸው ነገር የአገልግሎት አሰጣጡ ሲሻሻልና ህብረተሰቡ መንግስት በሚሰጠው አገልግሎት እርካታ ቢያገኝ የአገራችን ዕድገት ይፋጠናል የሚለውን ነው።

አገር  ስታድግ፣ ህዝብ ሲጠቀም እኔም እጠቀ ማለሁ የሚል አስተሳሰብ  መዳበር  ይኖርበታል። በአድልዎና  እምነትን በማጉደል ወዘተ... ለጊዜው ጥቅም ይገኝ ይሆናል።  ነገር ግን ዘላቂ እርካታ አይገኝም፣ አገር አይገነባም፣ ትውልድ አይታነጽም። በመሆኑም በታማኝነትና በቅንነት ህዝብና አገርን የማገልገል መንፈስ  መዳበር አለበት። ሁሉም በተሰማራበት የስራ መስክ  ሃላፊነቱን በአግባብ መወጣት ከቻለ አገር ትለወጣለች። የመንግስት ሰራተኞች ለሕዝቦችና ለአገራቸው  ያላቸውን ወገናዊነት የሚያሳዩት  በተሰማሩበት መስክ  በቅንነት፣ በታማኝነትና በቁርጠኝነት ማገልገል ሲችሉ ብቻ ነው። 

መንግሥታዊ አገልግሎቶች ለሕብረተሰቡ በሚፈለገው ጊዜ፣ መጠንና ቦታ የማይሰጥ ከሆነ ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌዎች በአግባቡ ተተግብረዋል ማለት አይቻልም።ኅብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን አገልግልቶች በህግ  የመጠየቅ መብት አለው፤ በሌላ በኩል የመንግስት ሰራተኞች  አገልገሎት የመስጠት ህጋዊ ግዴታ ወይም ሃላፊነት አለባቸው፡፡ በመሆኑም የመንግስት ሰራተኞች ተግባር የመንግሥት ፖሊሲዎች ማስፈፀሚያ ሥርዓት እንደመሆኑ ከላይ የተገለፁትን መርሆዎች መሰረት በማድረግ ውስጡ የሚታዩትን የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የሙስናና ብልሹ አሠራሮች ማስወገድ ይኖርበታል፡፡ ይህን ደግሞ እውን የሚያደርገው በእንደዚህ ያሉ የተሃድሶ መድረኮች ላይ በንቃት በመሳተፍ ብቻ ነው።

ለመልካም አስተዳደር  እንቅፋት የሆኑ  ለዘላቂ ልማት ስጋት የሚሆኑ ድርጊቶችን በማስወገድ ድህነትን ለማሸነፍ የመንግስት ሰራተኞች የስራ ስነምግባር  በሚያዘው መሰረት ማገልገል ይኖር ባቸዋል፡፡  ህዝብን በቅንነት  ማገልገል ህዝባዊ አደራን መወጣት በመሆኑ ታላቅ ኩራት ነው።ቃል የተገባውን  ህዝባዊ ተልዕኮዎች በታማኝነት  መወጣት ከተቻለ መልካም አስተዳደር ይሻሻላል። የአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓትም ይጎለብታል። የተጀመሩ የልማት ስራዎችም ይፋጠናሉ። ይህ ሲሆን  የመንግስት ሰራተኞች ህይወትም በዘላቂነት ይቀየራል።

ለሁሉም ዜጋ የመንግስትን አገልግሎት በእኩልነት የማግኘት ሕገ-መንግስታዊ መብት አለው። የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ድርጊት ልማትን የሚጎትቱ ከመሆናቸውም ባሻገር የሕዝቦችን በአንድነትና በሰላም የመኖር እሴት የሚሸረሽሩ  መሆናቸው የመንግስት ሰራተኞች ይህንን ተገንዝበው በጽኑ ሊታገሏቸው ይገባል፡፡ የሃይማኖት አክራሪነት፣ ጥበትና ትምክህት የስርዓቱ  አደጋዎች ተብለው የተለዩ  በመሆናቸው  የሁሉንም ትግል ይጠይቃሉ።

  አባ መላኩ 

Published in አጀንዳ

      ለአገርና ለወገን ከመሥራት ይልቅ በማይረባ ነገር  እርስ በእርስ መጠላለፍ፣ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አመለካከትና ልዩነትን አቻችሎ መንቀሳቀስ ያለመቻል፣ የራሳቸውን ችግር በማድበስበስ ህዝቡን ለማደናገር«መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ችግር እየፈጠረብን ነው» በማለት መግለጫ ለመስጠት አልቦዘኑም። ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሙጥኝ ያሉት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አካሔዳቸው ሊያስማማቸው ባለመቻሉ በየጊዜው እርስ በእርስ መበጣበጥ፣ አንዳቸው አንዳቸውን ለማዳመጥ ትዕግስት እያሳጣቸው መምጣቱና በቃላት እንጂ በተግባር የህዝብ ወገንተኛነታቸውን ማሳየት አለመቻላቸው በህዝቡ ዘንድ ታአማኒነትን እያሳጣቸው መጥቷል፡፡

       ይህ ሊደብቁት ያልቻሉት ገመናቸው በየጊዜው ሲያጋልጣቸውና የተጠናወጣቸው ኩርፊያ ብዙ አስቸጋሪና አሳፋሪ ድርጊቶችን እንዲያደርጉ እየገፋፋቸው የስብሰባ መድረክ እየረገጡ እንዲወጡ ሲያስገደዳቸው፤ አለያም የያዙት መስመር እንደማይሳካ ሲታወቃቸው ሰበብ ሲፈጥሩ ቆይተዋል፡፡

     የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ማየት የምንችለው በአገራችን የዕድገት ደረጃ ልክና በምናጣጥመው ሰላም  እንጂ በበለፀጉት አገሮች ልክ ከሆነ መነሻችንን ያለማወቃችን መድረሻችንን ለመገመት አዳጋች ያደርግብናል፡፡

      ከእኛ በብዙ ሁኔታ በተለይም በዴሞክራሲያዊ ስርዓት፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሱትና ለብዙ  ዘመናት በሰላም የኖሩት አገሮች ተሞክሮ የሚያሳየው ጥቂቶች እየጠፉ በመምጣታቸው ሳይሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ መብታቸውን ለማስከበር የተሻለ ሥርዓት መፍጠር በመቻላቸውእንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

       እንደሚታወቀው ሕገ-መንግሥታችን  በዋናነት ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎችን የመለሰ ነው፡፡ አንደኛው ለዘመናት የግጭት ምክንያት የሆነውን ስልጣንና ሀብት በማዕከልና በጥቂት ኃይሎች መከማቸት የፈጠረውን ችግር  የማህበራዊ ፖለቲካው  የህልውና ጉዳይ በመሆኑና ስልጣንና ሀብት በፌዴራል እና በክልሎች መካከል ፍትሐዊ  ማድረጉ፤ሁለተኛው ደግሞ የህዝቦችን የማንነት ጥያቄ ለመመለስ  ራሳቸውን የማስተዳደር የራሳቸውን ማንነት፤ቋንቋ፤እምነትና ታሪክ ለማሳደግና ወደ ቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችል መሆኑ ነው፡፡

     ከዚህ አንፃር በእኛ አገር የተዘረጋውን የዴሞከራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ከምርጫና ውክልና አንፃር ስንመለከተው መስመሩ ጠርቶ እናገኘዋለን፡፡ ታዲያ ለምን ሁሌም ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በገዢው ፓርቲ ላይ ተመሳሳይ ይዘት ያለው አቤቱታ ያሰማሉ? ችግሩ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ ፓርቲዎች ሊኖራቸው ከሚገባው ሚና የሚመነጭ እንደሆነ አብዛኞቹ የፖለቲካ ምሁራን ይስማማሉ፡፡

      በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የፖለቲካ ድርጅቶች በመንግሥት ደረጃ እውቅና አግኝተው ዜጎችም በነፃነት  ፓርቲ በመመስረት በፖለቲካ ሂደቱ መሳተፍ የጀመሩት ከ1983 ወዲህ ነው፡፡ አራት ዓመት የፈጀ የሽግግር ወቅት ከተደረገ በኋላ ከ1987 እስከአሁን ድረስ ደግሞ አምስት አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡እነዚህን አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫዎችን ከዴሞክራሲና ከህብር ፓርቲ መርሆ ጋር አገናኝተን ብንመረምር የተቃዋሚ ፓርቲዎቻችንን አሉታዊ ሚና ለመረዳት እንችላለን፡፡ በተለያየ ጎራ ተሰልፈው የሚገኙት እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደተቋም ሳይሆን በግለሰቦችና በጥቂት መሪዎች የሚሽከረከሩ ከህዝብ ጋር ጠንካራ ትስስር ያልፈጠሩ በመሆናቸው ምክንያት ገዢውን ፓርቲ በሚፈታተን መልኩ መውጣት አለመቻላቸው ለዴሞክረሲያዊ ስርዓት ግንባታው አስቸጋሪ ሁኔታ ነው፡፡ አሠራራቸው ዴሞክረሲያዊ አለመሆኑና እንወክልሃለን የሚሉትን ህዝብ ጥቅም ወደ ጎን በመተው የራሳቸውን የግል ወይም የቡድን ተልዕኮ ለማሳካት መንቀሰቀሳቸው ከህዝቡ ጋር ያላቸውን ትስስር እንዲዳከም ያደረገው በመሆኑ በዚህም በኩል ሚናቸው ምንም እንዲሆን አድርጎታል፡፡

      አልፎ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰፍኖ የምናየው የፖለቲካ አስተሳሰብ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ማለት ገዢው ፓርቲ የያዘውን ፖሊሲ መቃወም ብቻ የሚመስላቸው ኃይሎች የመኖራቸው ሁኔታ ሲሆን፤ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሕዝብ ከተመረጡ ነገ የመንግሥት ሥልጣን ተረካቢ የመሆን ዕድል ያላቸው ከመሆናቸው አንፃር ገዢውን ፓርቲ ከመቃወምና ከማብጠልጠል አልፈው ዘርዘር ያለና የሕዝብን ጥቅም የሚያረጋግጥ አማራጭ ፖሊሲና የነጠረ ሕዝባዊ አመለካከት ለህዝቡ መሸጥ ይገባቸው ነበር፡፡ ከዚህ ዓይነት ጭፍን አስተሳሰብ ያልተላቀቁት የፖለቲካ ኃይሎች ስልጣን ቢይዙስ ምን ያህል የተረጋጋና ዘለቄታዊነት ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ይኖረናል?የሚለውን ጥያቄም አብሮ ማሰቡ የግድ ይለናል፡፡

       ሌላው ችግር በተለያዩ ጎራ የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች የሚያሳዩት አደገኛ አመለካከት ማለትም ገዢውን ፓርቲ ለማድከም ሲባልና በህዝቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ለመቀነስ የተከተሉት ስልት ምርጫ በተቃረበ ቁጥር አልፎ አልፎ ከሂደቱ ራሳቸውን ማግለልና ደጋፊዎቻቸው እንዳይሳተፉ ቅስቀሳ ማድረግ፤አለያም የምርጫውን ትክክለኛና ሕጋዊ አካሄድ ማጣጣል፤ ፓርላማ አንገባም በማለት የፖለቲካ ሂደቱን ለማዳከም መሞከራቸው ነው፡፡ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቋቋሙበት ዋና ምክንያት(ዓላማ) ደጋፊያቸውንና አባላቸውን በአንድ የፖለቲካ ዓላማ ስር በማደራጀት፤በማስተማርና በመምራት በምርጫ ጊዜ ወሳኝ ሆነው መውጣትና በሕዝብ ምርጫ የፖለቲካ ስልጣን መያዝ ነው፡፡ ሆኖም በየጊዜው ምርጫ በተቃረበ ቁጥር በአመዛኙ የምናየው ሂደቱን የመኮነንና በተለያዩ መንገዶች ለማሰናከል መጣር ነው፡፡

      ለዚሁ በተደጋጋሚ የሚቀርበው መልስ የፖለቲካ ምህዳሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጥበብና በክልሎች አካባቢ የተመቻቸ የፖለቲካ ሁኔታ አለመኖሩ ነው፡፡ ይህ ሰበብ እውነትም ብቸኛ ምክንያት ከሆነና የተወሰነ እውነትነት ካለው ገዥው ፓርቲ ዴሞክራሲ ሥርዓቱ ሁሉን አቀፍ እንዲሆንና ስር እንዲሰድ በክልሎች አካባቢ የሚታየውን  ችግር በጊዜ መፍትሔ በመስጠት የዴሞክራሲ ሂደቱ እንዲጎለብት የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡

       በዚህ ምክንያትም ነው ባለፈው ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ  በመንግሥት/ኢህአዴግና በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ውይይት እንደሚካሄድ የገለጹት፡፡

     የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመም በሕዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን መክፈቻ ላይ  የመንግሥትን የዓመቱን የሥራ ክንውን በሚያመለክተው ንግግራቸው ይህንኑ ጉዳይ አንስተው እንደነበረ ይታወሳል። ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው የምርጫ ሕጉን ለማሻሻል መንግሥት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀው ነበር።

      ያ ቃል በተገባው መሠረት በኢህአዴግ ጋባዥነት ጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም በተካሄደ ቅድመ ድርድር ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቡዕ የካቲት 8ቀን 2009ዓ.ም የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ)ና 21 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ወደ ክርክርና ድርድር ለመግባት በሚያስችላቸው የደርድር አካሄድ ሥነ ስርዓት ማእቀፍ ላይ ውይይት አካሂደዋል። ፓርቲዎች ለዚህ ዓይነቱ ውይይት ያበቃቸውን ህገ መንግሥታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አክብረው ፣ መንግሥትና ገዢው ፓርቲ በአገር አቀፍ ደረጃ ያከናወኗቸውን ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች በመገንዘብ እነርሱም የልማት ሥራው ተሳታፊ በመሆን ለልማት ሥራው አጋዥ የሚሆኑበትን አቅጣጫ መያዝን ልብ ሊሉት ይገባል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

በአዲስ አበባ በመገንባት ላይ ያሉ ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃዎች ሲጠናቀቁ መዲናዋ ፅዱና አረንጓዴ እንደምትሆን ከንቲባ ድሪባ ኩማ ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን እየተከናወኑ ከሚገኙ ዘመናዊ የፍሳሽ መሰረተ ልማት ሥራዎች በተለይም የመካኒሳ ቆጣሪና የቃሊቲ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች፣ የኮዬ ፈጬ ያልተማከለ ፍሳሽ ማጣሪያና  የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክቶች የግንባታ  ፕሮጀክቶች ትናንት ተጎብኝተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ግንባታዎች ሲጠናቀቁ መዲናዋን ፅዱ እና አረንጓዴ እንደሚያደርጓትና የከተማዋ ዘመናዊነት የሚረጋገጠው በዘመናዊ የፍሳሽ አገልግሎት በመሆኑ ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት እየተካሄዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶቹ በከተማዋ 70 በመቶ የሚሆነውን ነዋሪ ሙሉ በሙሉ በቀጥታ ከዘመናዊ የፍሳሽ መስመር ጋር በማገናኘት በመኪና የሚሰጠውን አገልግሎት ያስቀራል ያሉት ከንቲባው «ከተማዋን ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ጋር ከማስተሳሰር ባሻገር አገሪቱ ከሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ግንባር ቀደም እንድትሆንም የሚያግዛት ነው» ብለዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ኃይለማርያም በበኩላቸው «ከዚህ ቀደም የነበረው የፍሳሽ ማንሳት አገልግሎት ከከተማዋ ዕድገትና አቅም አንፃር እንደማይመጥን ጠቅሰው፣ በግንባታ ላይ የሚገኙት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ግን ከተማዋ የተሻለ የመስመር ፍሳሽ የማንሳት አቅም እንደሚኖር ገልፀዋል።

ፕሮጀክቶቹ በትልልቅ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የህብረተሰቡን የፍሳሽ ማንሳት ጥያቄ በማስተናገድና ተጣርቶ የሚወጣው ውሃ ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውል ይደረጋል ያሉት ሥራ አስኪያጁ በቀጣይም በከተማዋ ኃይቆች እንዲፈጠሩ በማድረግ ለከተማዋ መናፈሻና ውበት እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።

ሥራ አስኪያጁ አክለውም «ፕሮጀክቱ በቴክኖሎጂ ደረጃው በአገሪቱና በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው» ሲሉ ተናግረዋል።

በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች በመስመርም ሆነ በተሽከርካሪ የሚሰበሰበው ፍሳሽ በጥቅሉ 18 ሺ ሜትር ኪዩብ  የሚሆነው በሰባት ማጣሪያ ጣቢያዎች እየተጣራና እየተወገደ ይገኛል።

ግንባታው 54 በመቶ የደረሰው የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያና የፍሳሽ መስመር በቀን 100 ሺ ሜትር ኪዩብ የማጣራት አቅም ሲኖረው ፕሮጀክቱም በ2010 ዓ.ም ይጠናቀቃል። ለፕሮጀክቱ የተመደበው አጠቃላይ በጀትም 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ነው።

በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የሚከናወነው ያልተማከለ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች ግንባታም በቀን 27 ሺ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ የማጣራት አቅም ይኖረዋል።

ለፕሮጀክቶቹ ማስፈፀሚያ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በመንግሥት የተመደበ ሲሆን፣ ግንባታው በ2009 ዓ.ም መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የተመደበለት የኮዬ ፈጬ ያልተማከለ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ፕሮጀክት ደግሞ በቀን 33 ሺ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ የማጣራት አቅም ያለው ሲሆን በመገንባት ላይ የሚገኙ ከ50 ሺ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የዘመናዊ የፍሳሽ መስመር ተጠቃሚ ያደርጋል።         

Published in የሀገር ውስጥ

የተፋሰስ ልማት ተፈጥሮን ባለበት በማቆየት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባታ መሰረት የሆነ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ነው፡፡ አፈር በጎርፍና በነፋስ ተጠርጎ እንዳይሄድ በሥነ-ሕይወታዊ ዘዴ በመታገዝ የአፈርን ለምነትና የስነ-ምህዳርን ሚዛን የመጠበቅም ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ተራራማ የሆኑና ለእርሻ አመቺ ያልሆኑ ቦታዎችን ወደ ገቢ ምንጭነት በመቀየር ‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ› እንዲሉ ለበርካቶች የሥራ ዕድል እየፈጠረ እንደሚገኝ በርካቶች ይስማማሉ፡፡ በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ እንድብር ከተማ ግራር ቀበሌ በጎታም ንዑስ ተፋሰስ የሚገኙ ወጣቶች ለዘመናት ለምንም አገልግሎት ይውል ያልነበረንና የጎርፍ፣ አፈር መሸርሸርና የመሬት መናድ ያጋጠመውን 150 ሄክታር ተዳፋት መሬት ለተከታታይ አምስት ዓመታት የተፋሰስ ሥራ በመስራት የተራቆተውን አካባቢ መልሶ እንዲያገግም በማድረግ ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

በቸሃ ወረዳ እንድብር ከተማ ግራር ቀበሌ ንብ በማነብ ሥራ ከተደራጁ ወጣቶች አንዱ የሆነው ወጣት አርሶ አደር ሚፍታህ ሁሴን እንደሚለው፤ አካባቢው ለበርካታ ዓመታት ከብት ይውልበት የነበረ በመሆኑ መሬቱ የተጎዳ፣ ምንም ዓይነት የዕጽዋት ዘር የማይታይበት፣ የመሬት አቀማመጡም ተዳፋት በመሆኑ አፈሩ በጎርፍ እየተሸረሸረ የሚገኝ ነበር፡፡ ሆኖም የአካባቢውን መጎዳት ተከትሎ የጉራጌ ዞን ከቸሃ ወረዳ ጋር በመተባበርና ህብረተሰቡን በማስተባበር የተፋሰስ ልማት እንዲሰራና አካባቢው እንዲጠበቅ በማድረጉ በአሁኑ ወቅት ተፈጥሮን ከመጠበቅ ባሻገር 13 የቀበሌዋ ወጣቶች በንብ ማነብ ሥራ ተደራጅተን እንድንሰራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

ተራራማ የሆኑ ቦታዎች ለግብርና ምቹ ባለመሆናቸውና ጥቅም ላይ ይውላሉ ብለን ባለማሰባችን 150 ሄክታር የሚሸፍነው ቦታ ለበርካታ ዓመታት አፈሩ ሲሸረሸር፣ አካባቢው ወደ  ገደልነት ሲቀየርና ተፈጥሯዊ ውበቱን አጥቶ ምድረ በዳ ሲሆን ተመልክተናል የሚለው ወጣት ሚፍታህ፤ የተሰሩ የተፋሰስ ሥራዎች ለአካባቢው ወጣት ተስፋ የሚያደርግበት ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ ሌሎች ቦታዎችንም እንዲያማትር አመላክቷል ይላል፡፡    

መሬቱ ከጉዳት አገግሞ ወደነበረበት እንዲመለስ ለአምስት ዓመታት የተፋሰስ ልማት ሥራ መሰራቱንና አካባቢውን በአጥር በመከለል እንዲጠበቅ መደረጉን የሚገልጸው ወጣት ሚፍታህ፤ ለንብ ማነብ ሊጠቅሙ የሚችሉ አበባዎችን፣ የተለያዩ ዕጽዋቶችንና አፈሩን ቆንጥጠው ሊይዙ የሚችሉ ዛፎችን በማልማት መሬቱን ወደነበረበት መመለስ እንደተቻለ ያስረዳል፡፡ በተለይም ወጣቶቹ ተደራጅተን በሰቀልናቸው 23 ዘመናዊ እና 13 ባህላዊ የንብ ቀፎዎች በተሰቀሉ በሳምንት ውስጥ በ16ቱ ቀፎዎች ንብ ሊገባባቸው ችሏል፡፡ ይህም አካባቢው ነፋሻማ ከመሆኑ ባሻገር ለንብ ማነብ ሥራ አመቺ መሆኑንና ከወራት በኋላ ምርት የማግኘት ተስፋ እንዳለው አመላካች ነው ሲል ይገልፃል፡፡

በካንጋሮ ጫማ ፋብሪካ በቅጥር፣ መርካቶ ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን እንዲሁም በግል ሥራ ተሰማርቶ በድምሩ ለ18 ዓመታት አዲስ አበባ ውስጥ መስራቱንና ይጀመራቸው ሥራዎች በሙሉ ሊያዋጡት  ባለመቻላቸው ወደ ገጠር ተመልሶ የግብርና ሥራ ሲሰራ ያገኘነው ወጣት መውለድደግ ወልደገብርኤል፤ ህይወቴን ለመቀየር አካባቢዬን ለቅቄ ከሄድኩበት ጊዜ ጀምሮ ለ18 ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ ከቅጥር ጀምሮ እስከ ግል ንግድ ብንቀሳቀስም የከተማ ሕይወት ‹ሞላች ጎደለች› በመሆኑ ራሴን መቀየር አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ ወደ ገጠር ተመልሼ በግብርና ሥራ የተሰማራሁ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ድንችና የጓሮ አትክልት በስፋት እያመረትኩ ነው፡፡ በተጨማሪም በተፋሰስ ልማት ሥራ ወደ ጥቅም በተቀየረው በጎታም ንዑስ ተፋሰስ ግራር ቀበሌ ከአካባቢዬ ልጆች ጋር በመደራጀት የንብ ማነብ ሥራም እየሰራሁ ነው፡፡ ሥራው ጅማሬ ላይ ቢሆንም ወደፊት አዋጭ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ ይላል፡፡

በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሃብትና አነስተኛ መስኖ ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሺከታ ገብረሰንበት፤ አካባቢው በተፋሰስ ልማት ወደነበረበት ከመመለሱ በፊት በጣም የተጎዳና ከጥቅም ውጪ ሆኖ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በመሬቱ ምንም ዓይነት ዕጽዋት ያልነበረበትና አፈሩ እየተሸረሸረ የሚሄድበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ወረዳው ከዞን ጋር በመሆንና ህብረተሰቡን በማሳተፍ በመሰራቱ መሬቱን ወደነበረበት ከመመለስ ባሻገር ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል በማለት ያብራራሉ፡፡

ከአርሶ አደሩ ጋር በተሰራው ሰፊ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ችግኝ እንዲተከልበት በማድረግና ከብት እንዳይገባ በማጠር ወደነበረበት መመለስ ተችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት አካባቢው መቶ በመቶ በዕጽዋት እንዲሸፈን የተደረገ ሲሆን፤ ከአገር በቀል የዕጽዋት ዝርያዎች ዝግባ፣ የአበሻ ጥድ፣ ጥቁር እንጨት፣ ኮሶ ተተክለው ማደጋቸውንና ከውጭ ከመጡት ደግሞ ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት ሳይኖረው ከሌሎች ጋር አብሮ መብቀል የሚችል ግራቪሊያ የተባለ ዛፍና ሌሎች አበባዎች እንደሚገኙ አቶ ሺከታ ይገልጻሉ፡፡

አርሶ አደሩ የተፋሰስን ሥራ ጠቀሜታ በተገቢው ሁኔታ በመረዳቱ የተጎዱ ቦታዎችን እየመረጠና እየሰራ ያለበት ሁኔታ መፈጠሩንና በተሰሩ ልማቶች ላይ የጋራ ህግ በማውጣት እየጠበቃቸው መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሺከታ፤ ከብቶች ግጦሽ ፍለጋ በየአቅጣጫው ሲንቀሳቀሱ ጉልበታቸውን ከመጨረስ ጀምሮ፣ ክብደታቸውን በመቀነስ የወተት ምርት ሊሰጡ እንደማይችሉ በመገንዘብና ሊደርስባቸው የሚችለውን ጉዳት በማመዛዘን ከብቶቹን አስሮ በመቀለብ እያረባ ይገኛል፡፡ እንዲሁም ወጣቶቹ የተፋሰስ ልማት ሥራን ጠቀሜታ በመረዳት ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ ያልዋሉ ቦታዎችን እየፈለጉ ወደ ገቢ ምንጭነት እየቀየሩ ሲሆን፤ ወረዳው የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው የሚሉት፡፡

በመጥረቃት ንዑስ ተፋሰስ ጆካ ቀበሌ ሲሰራ ያገኘሁት ወጣት አርሶ አደር ዘርጋ ቴኒ፤ ለአምስት ጊዜ በተሰሩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች በርካታ ቦታዎች መልማት የቻሉ ሲሆን፤ ወደ ገቢ ምንጭነት ለመቀየር የከብት ግጦሽ፣ የድንች ብዜትና ንብ የማነብ ሥራዎችን ወጣቱ በመደራጀት እየሰራ ነው፡፡ ይህም አገልግሎት አይሰጡም የተባሉ መሬቶች ወደ ልማት እንዲገቡ አድርጓል ይላል፡፡  

በጉራጌ  ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ እና የተፈጥሮ ሃብት ልማትና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አለምነሽ ባዴ፤ በዞኑ የሚሰሩ የተፋሰስ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ለወጣቱ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ከማድረግ አኳያ ክፍተቶች አሉ፡፡ ከዚህ በፊት 869 ተፋሰሶች የለሙ ቢሆኑም ሙሉ በሙሉ ወጣቱ እየተጠቀመባቸው አይደለም በማለት ያስረዳሉ፡፡

ወይዘሮ አለምነሽ እንደ ግራርና ጆካ ቀበሌ ወጣቶች ዓይነት ጅምር ሥራዎች ለመስራትና አጠናክሮ ለማስቀጠል እንዲሁም በገጠር የሚኖረውን ወጣት ተጠቃሚ ለማድረግ በተፋሰስ የሚለሙና ለእርሻ አመች ያልሆኑትን የእንስሳት መኖ እንዲመረትባቸው፣ ነፋሻማ ቦታዎችን አስፈላጊ ግብዓት በማሟላት የንብ ማነብ ሥራ እንዲሰራባቸው እንደሚደረግና በበጀት ዓመቱ እንደ ዞን 120 ሺ 677 ሄክታር መሬት የተፋሰስ ልማት ለመሥራት መታቀዱን፣ ይህን ሊያሳካ የሚችል 502 ሺ 274 አርሶ አደር መመረጣቸውን፣ ከዚህ ውስጥም 68 ሺ 814 ወጣት አርሶ አደሮች መሆናቸውን፣ የተፋሰስ ልማት ሥራውን በተገቢው ሁኔታ ለማከናወንም ከሰው ኃይል፣ ከቦታ መረጣና ከግብዓት አቅርቦት አኳያ አጠቃላይ ቅድመ ዝግጅት በመደረጉ ስራው በ13ቱ ወረዳ በ412 ንዑስ ተፋሰሶች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፤ እስካሁንም 25 በመቶ ሥራው ተሰርቷል ብለዋል፡፡ 

ዜና ሐተታ

ዑመር እንድሪስ

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።