Items filtered by date: Thursday, 02 February 2017

 

የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ዕውቅና ከሰጣቸው የአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል አንዱ የጃንሜዳ ዓለም አቀፍ የአገር አቋራጭ ውድድር ነው። በየዓመቱ የሚደረገው ይህ ውድድር ዘንድሮም ለ34ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፤ አስተናባሪዎቹ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ ነው። በዚህ ውድድር ላይ ታዋቂ አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በርካታ ስመጥር አትሌቶችን ባፈራው ጃንሜዳ ከ1975.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዓመታዊ ውድድር መካሄድ ጀመረ። ዓለም አቀፍ ውድድር ሆኖ እንዲቀጥል እውቅና በማግኘቱ በየዓመቱ በጥርና የካቲት ወራት በመካሄድ ላይ ይገኛል። የዘንድሮው ሻምፒዮናም በመጪው ወር መጀመሪያ የሚካሄድ ሲሆን፤ ተሳታፊ የሚሆኑ አትሌቶች ምዝገባም በነገው ዕለት የሚጠናቀቅ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአገር አቋራጭ ውድድሩ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑት ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ክለቦች፣ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት፣ የግል አትሌቶች፣ አንጋፋ አትሌቶች እንዲሁም የውጭ አገር አትሌቶች መሆናቸውንም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ትናንት በብሄራዊ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። በሻም ፒዮናው ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉ ጎረቤት አገራትም ጥሪ ተደርጓል።

በአገር አቀፍ ውድድሮች ላይ በተለይ የተለመደው የታዋቂ አትሌቶች ተሳትፎ ማነስ በጃንሜዳ ዓለም አቀፍ የአገር አቋራጭ ውድድርም ላይ ከዚህ ቀደም የሚስተዋል ነው። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ይህንን ለመቅረፍ፤ በርዋንዳ በሚካሄደው የአፍሪካ አገር አቋራጭ ውድድር ተሳታፊ ለመሆን በዚህኛው ውድድር መሳተፍን እንደ አንድ መስፈርት አስቀምጧል። በመሆኑም በአህጉር አቀፍ ውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ተሳታፊ የሚሆኑት፤ በጃን ሜዳው ውድድር ላይ የላቀ ብቃት በማሳየት አሸናፊ ከሆኑት አትሌቶች መካከል ተመርጠው ነው። ፌዴሬሽኑ ከዚህ ባሻገር ተሳትፎውን ለማበረታታት ያግዛል በሚል ቀድሞ የነበረውን የአሸናፊዎች የገንዘብ ሽልማት መጠን በእጥፍ አሳድጎታል።

የካቲት 5 ቀን 2009.ም ፤ በ6ኪሎ ሜትር የወጣት ሴቶች፣ 8ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች፣ በ10ኪሎ ሜትር የአዋቂ ወንድ እና ሴቶች እንዲሁም በ8ኪሎ ሜትር የድብልቅ ሪሌ የውድድር ዓይነቶች አትሌቶች ይፋለማሉ።

 

ብርሃን ፈይሳ

 

 

Published in ስፖርት

ዝውውር ከፈጸሙት ተጫዋቾች መካከል ፤

 

የፈረንጆችን አዲስ ዓመት መግባት ተከትሎ የሚከፈተው የጥር ወር የዝውውር መስኮት ትናንት ተዘግቷል፡፡ በዘንድሮው የዝውውር መስኮት ኃያላን ክለቦች ድምጻቸውን አጥፍተው በዝምታ ሲያሳልፉት ያልተጠበቁ ክለቦች ደግሞ ካዝናቸውን ፈትሸው ክለባቸውን የሚያጠናክሩ ተጫዋቾች አዘዋውረዋል፡፡ ለዛሬ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በጥር ወር የተካሄዱ ዋና ዋና ዝውውሮችን እንመለከታለን፡፡

ትናንት በተዘጋው 2017 የዝውውር መስኮት ከአንደኛ እስከ አራተኛ ‹‹ቢግ ፎር›› የሚገኙ የሊጉ ተፎካካሪ ክለቦች ስም ያላቸውን ተጫዋቾች አላዘዋወሩም፡፡ በሊጉ አናት ላይ የሚገኙት ቼልሲዎች ቀደም ሲል በውሰት የሰጧቸውን ናታን ኤኬን እና ፓትሪክ ባምፎርድን ከመመለስ ውጪ አዲስ ተጫዋች አላስፈረሙም፡፡ በአንጻሩ አንቶኒዮ ኮንቴ ጆን ኦቢ ሚካኤል እና ብራዚላዊውን ኦስካር ጨምሮ 11 ተጫዋቾችን በሽያጭና በውሰት ለተለያዩ ክለቦች ለቀዋል፡፡

በተመሳሳይ በፕሪሚየር ሊጉ ሰንጠረዥ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የሰሜን ለንደኑ ቶትንሃም ምንም አዲስ ተጫዋች አላስፈረመም፡፡ በተቃራኒው አራት ተጫዋቾችን አሰናብቷል፡፡ ከትናንት በስቲያ በዋትፎርድ አስደንጋጭ ሽንፈት አስተናግዶ ከሻምፒዮንነት ተሳትፎ ያፈገፈገው አርሰናል በበኩሉ ውጤታማ ተጫዋችን ያስፈርማል ተብሎ ቢጠበቅም ከ40 ሺ ፓውንድ በላይ ሳያወጣ ኮሃን ብራማልን ማስፈረሙ በዝምታ ከማለፍ ይሻላል ያለ ይመስላል፡፡ ሰባት ተጫዋቾችን ደግሞ በውሰት እና በሽያጭ ለቋል፡፡ ከነዚህ መካከል ኢትዮጵያዊ ዝርያ ያለው ጌድዮን ዘላለም አንዱ ነው፡፡

አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የመርሲሳይዱ ሊቨርፑል በበኩሉ አምስት ተጫዋቾችን ከክለቡ አሰናብቶ ምንም ተጫዋች ወደ ክለቡ አላመጣም፡፡ የፔፕ ጋርዲዮላው ማንቸስተር ሲቲ ዋንጫውን የማንሳት ግምት ከተሰጣቸው ክለቦች ውስጥ በተሻለ በዝውውር የተሳተፈ ክለብ ነው፡፡ ቀደም ብሎ ገብሬል ጂሰስን ከብራዚል ክለብ በ27 ሚሊዮን ፓወንድ ዝውውሩን ቢጨርስም ወደ ክለቡ ያመጣው ግን በዚህ ወር ነበር፡፡ ከጂሰስ በተጨማሪ ያኔል ሄሬራን ከአትሌቲኮ ቬንዙዌላ በእጁ አስገብቷል፡፡ ማንቸስተር ሲቲ ሰባት ተጫዋቾችን ያሰናበተ ሲሆን፣ ለገብሬል ጂሰስ ያወጣው 27 ሚሊዮን ፓወንድም የጥር ወር ውዱ ዝውውር ሆኗል፡፡

ማንቸስተር ዩናይትዶች በዚህ የዝውውር መስኮት ምንም ተጫዋች አላስፈረሙም፡፡ በተቃራኒው ቀያዮቹ ሰይጣኖች ሞርጋን ሼንደርሊንን ለኤቨርተን በ22 ሚሊዮን ፓወንድ እንዲሁም ሜምፒስ ዲፓዬን ለሊዮን ብቃቱ እየታየ እስከ 21 ሚሊዮን ፓውንድ በሚደርስ ክፍያ ሸጠው 43 ሚሊዮን ፓውንድ የሚሆን የተጣራ ገንዘብ በማስገባት ትርፋማ ክለብ ሆነዋል፡፡

ኤቨርተን ለሉክማን እና ለሼንደርሊን በድምሩ 33 ሚሊዮን ፓውንድ በማውጣት የተሻለ የተንቀሳቀሰ ክለብ ነው፡፡ ስቶክ ሲቲ ለሁለት ተጫዋቾች 25 ሚሊዮን ፓውንድ በማውጣት የተሻለ ተሳትፏል፡፡ ስቶክ ሊ ግራንትን ከደርቢ ካውንቲ በ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲሁም ሳይዶ ቤራሂኖን ከዌስትብሮሚች አልቪዮን በ12 ሚሊዮን ፓውንድ አዘዋውሯል፡፡ ክሪስታል ፓላስ ለሦስት ተጫዋቾች 29 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ ማድረጉን ከተለያዩ ድረ ገጾች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ሚድልስቦሮም ቢሆን ለሦስት ተጫዋቾች 16 ሚሊዮን ፓውንድ አውጥቷል፡፡

የአምናው ሻምፒዮን ሌስተር ሲቲ ዊልፍሬድ ንዲዲን ከጄንክ በ15 ሚሊዮን ፓውንድ የግሉ አድርጓል፡፡ ሊዊስ ሄርናንዴዝን ጨምሮ አምስት ተጫዋቾችን በነጻና በውሰት አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ የመውረድ አደጋ የተጋረጠበት ሰንደርላንድ በአዳዲስ ተጫዋቾች ክለቡን ከማጠናከር ይልቅ ፓትሪክ ቫን አንሆልትን በ12 ሚሊዮን ፓውንድ ለክሪስታል ፓላስ አሳልፎ መስጠቱ መውረዱን ቀድሞ ያመነ ይመስላል፡፡

ባለፈው ዓመት ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን ችሎ በዚህ ዓመት መቀዛቀዝ ያሳየው የለንደኑ ዌስትሃም ዩናይትድ ራሱን ለማጠናከር የሚያግዙ ሦስት ተጫዋቾች ወደ ክለቡ አምጥቷል፡፡ የተከላካይ ችግሩን ለመቅረፍ ጆዜ ፎንቴን ከሳውዛአምፕተን በ8 ሚሊዮን ፓወንድ፣ ሮበርት ስኖግራስን ከሁል ሲቲ በ11 ሚሊዮን ፓወንድ እንዲሁም ናታን ሆላንድን ከኤቨርተን በነጻ አግኝቶ ክለቡን አጠናክሯል፡፡

ባለፈው ክረምት ከ1 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ለተጫዋች ዝውውር ወጪ ያደረጉ የእንግሊዝ ክለቦች በጥር ዝምታን መምረጣቸው አስገርሟል፡፡ በዚህ የዝውውር መስኮት ከ200 ሚሊዮን ፓውንድ የማይበልጥ ክፍያ ለተጫዋቾች መውጣቱም በንጽጽር ቀርቧል፡፡

 

ታምራት አበራ

 

 

Published in ስፖርት

     

አቶ ፋሲል መንበረ ፤                                 አቶ ደረጀ ሀብቱ ፤

 

ቼስ ስፖርት ነው? በሚል ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ሲነሱ እንሰማለን፡፡ በስፖርቱ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች ግን ቼስ ከስፖርትም በላይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ቼስ የመጫወቻ ቦርድ በማዘጋጀት በሁለት ተጫዋቾች መካከል የመጫወቻ ምልክቶቹን በማንቀሳቀስ የሚደረግ ነው። «በፍጹም ታማኝነት እና አርቆ አስተዋይነት የሚደረግ ፍልሚያ» በመሆኑ ከስፖርት ተርታ እንደሚያስመድበውም እነዚሁ ባለሙያዎች ሲገልጹ ይሰማል፡፡

ቼስ እንደ ሌሎች የስፖርት ዓይነቶች አካልን ገንብቶ ጡንቻን አያዳብርም። ሆኖም ከፍተኛ የማሰብ አቅምን የሚያጎለብት፣ ከአራት እና ከአምስት እንቅስቃሴዎች በኋላ ማረፊያ መወሰንን የሚጠይቅ ነው። በማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄ መሻት መቻልን የሚያጎናጽፍ (ጨዋታው ብልህነትን እና አርቆ አስተዋይነትን ስለሚጠይቅ) ጭምር ነው። ከዚህም ሌላ ሰፊ የመዝናናት ዕድልን የሚፈጥር፣ የዕድሜ ገደብ የሌለው እና ለጡረታ የማይዳርግ ስፖርት ነው። በአጠቃላይ ከውስንነት የጸዳ መሆኑ ከስፖርትነቱ ባሻገር ከፍተኛ የመዝናናት ዕድል የሚፈጥር ጨዋታ እንደሆነ የጨዋታው ተቆርቋሪዎች ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለስፖርት ዘርፍ በሰጠችው ሰፊ ትኩረት በርካታ ነባር ስፖርቶች የተሻለ መጠናከር እና መስፋፋት እያሳዩ ነው። ቁጥራቸው የማይናቅ አዳዲስ ስፖርቶችም እውቅና ተሰጥቷቸው የተሻለ ተዘውታሪነት እንዲያገኙ በጀት ተመድቦላቸዋል። ህጋዊ መሰረት ባይዝም ለረጅም ዓመት ሲዘወተር የነበረው ቼስ ስፖርት፤ በቅርቡ ትኩረት ከተሰጣቸው ስፖርቶች ውስጥ ተጠቃሽ ነው።

የማህበረሰብን የአስተሳሰብ ደረጃ በማሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለውን ቼስ ስፖርት በመላ ሀገሪቱ ለማስፋፋት ስፖርቱ ከተዘውታሪ ስፖርቶች ተርታ ለማስመደብ በኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን በኩል ጅምር ጥረቶች ይታያሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ ባለፉት ዓመታት ቼስን ለማሳደግ የአቅሙን ቢጣጣርም በርካታ እንቅፋቶች ግን ሳያጋጥሙት አልቀሩም። ፌዴሬሽኑ ባሳለፍነው ዓመት አካሂዶት በነበረው ጠቅላላ ጉባዔ አፈጻጸሙን ሲገመግም በርካታ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እንዳሉም አምኖ ወደ ሥራ ለመግባት ቃል መግባቱ ይታወሳል፡፡

ባሳለፍነው ዓመት ጠቅላላ ጉባዔውን ያደረገው የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን አዳዲስ ሥራ አስፈ ጻሚዎችን ሲመርጥ፤ ዓለም አቀፍ ዳኞችን እና አሰልጣኞችን በማፍራት በኩል በትኩረት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡ በመሆኑም የፌዴሬሽኑ አዳዲስ ሥራ አስፈጻሚዎችም በጠቅላላ ጉባዔው የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት ሰሞኑን የዳኝነት ስልጠና መስጠት ጀምረዋል፡፡

ቀደም ሲል በፌዴሬሽኑ የተሰጠውን የአንደኛ ደረጃ የዳኝነት ስልጠና ወስደው በዳኝነት ሥራ ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎችን ብቻ በአሳተፈው በዚህ ስልጠና ላይ ከስድስት የተለያዩ ክልሎች እንዲሁም የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 17 ዳኞች፤ የሁለተኛ ደረጃ የዳኝነት ስልጠና እየወሰዱ መሆኑን ፌዴሬሽኑ በአደረሰን መረጃ አስታውቋል፡፡

አዲስ አበባ በሚገኘው ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ከጥር 22 ቀን 2009.ም ጀምሮ እየተሰጠ ባለው ስልጠና ላይ ደቡብ ክልል እና ትግራይ ክልል እያንዳንዳቸው አራት ዳኞችን በመላክ ተሳትፏቸውን አሳይተዋል። በዚህ ስልጠና ላይ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ አማራ ክልል፣ ኦሮሚያ ክልል እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሌሎች ዳኞችን የላኩ ተሳታፊ ክልሎች መሆናቸውንም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡

የዝግጅት ክፍላችን የስልጠናውን ሁኔታ ለመዳሰስ ትናንት በአካዳሚው ተገኝቶ ነበር። ተሳታፊዎችንም በስልጠናው ዙሪያ አነጋግረናል። የሃዋሳ ከተማ ቼስ ዳኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ፋሲል መንበረ በዚህ ስልጠና ላይ ከተሳተፉት ውስጥ ይገኙበታል። በጉዳዩ ዙሪያ ስናነጋግራቸው፣ ቼስ ስፖርት በደቡብ ክልል በስፋት እየተዘወተረ መሆኑን ገልፀውልናል። ስልጠናውን መውሰዱም በቀጣይ ዓለም አቀፍ ዳኛ የመሆን ህልማቸውን ለማሳካት እንደሚያግዝ በአስተያየታቸው ላይ ተናግረዋል። በተጨማሪ ስልጠናው በተግባር እና በንድፈ ሃሳብ እየተሰጣቸው መሆኑን የጠቆሙት አቶ ፋሲል፤ ለዳኝነት ሥራቸው አጋዥ የሆነ እውቀት ማግኘታቸውን ይናገራሉ፡፡

« የቼስ ዳኝነት የግል እይታንም የሚፈልግ በመሆኑ በንድፈ ሃሳብ የተደገፈ ስልጠና መውሰዳችን ተጠቃሚ ያደርገናል» ያሉት ሰልጣኝ አቶ ፋሲል በስልጠናው ላይ አዳዲስ ዓለም አቀፍ ህጎች መካተታቸው ወጥ የሆነ ዳኝነት እንዲታይ እንደሚያግዝም ነው የተናገሩት፡፡

ሰልጣኝ አቶ ፋሲል አክለውም የሰዓት አጠቃቀምን ጨምሮ ከበርካታ አዳዲስ ህጎች ጋር የመተዋወቅ ዕድል ማግኘታቸውን ተናግረዋል። ወደ ክልላቸው ሲመለሱም ተተኪ ዳኞችን ከማፍራት ባሻገር ቼስ ስፖርት ይበልጥ ተስፋፍቶ ተወዳጅ እንዲሆን በማድረግ በኩል ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

«በዚህ ስልጠና ላይ የተሻለ ውጤት ካመጣሁ ኢንተርናሽናል ዳኛ መሆን እችላለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ የቼስ ፕሮጀክት የማቋቋም ዕቅድ አለኝ፡፡ በምኖርበት አካባቢም ተተኪ ዳኞችን በማፍራት አቅማቸውን የማጎልበት ሥራ ለመስራት አስቤያለሁ» ያሉት አቶ ፋሲል፣ እነዚህን ሁሉ እቅዶች እውን ለማድረግ ከባድ ፈተና የሆነውን የማዘውተሪያ ስፍራ እና የቁሳቁስ ችግር በመቅረፍ በኩል ግን የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡት አሳስበዋል፡፡

«ከዚህ በፊት በየክልሉ ብዙ የቼስ ውድድሮች ሲካሄዱ ዳኞች የሚወስኗቸው ውሳኔዎች ወጥነት ይጎድላቸው ነበር፡፡ ይህ ችግር ግን ሰሞኑን እየተሰጠን ባለው ስልጠና እንደሚቀረፍ ሙሉ እምነት አለኝ» የሚሉት ደግሞ በአማራ ክልል ቼስ ፌዴሬሽን ድጋፍ ከዋግ ኸምራ ዞን የመጣው አቶ ደረጀ ሀብቱ ናቸው፡፡

ባለፉት ዓመታት ያሳለፏቸው የዳኝነት ሥራዎች በስህተት የታጀቡ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ደረጀ፤ የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን ዳኞችን ለማብቃት በሰጠው ሰፊ ትኩረት ወጥነት ያላቸው እና ዓለም አቀፍ አዳዲስ ህጎችን ያካተቱ ስልጠናዎች መስጠቱን አድንቀዋል። ስልጠናዎቹ ቀጣይነት እንዲኖራቸውም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አቶ ደረጀ አክሎም አማራ ክልል በቅርቡ ለቼስ ስፖርት በሰጠው ትኩረት በሴቶች ተሳትፎው ውጤታማ መሆኑን ጠቁመው፣ ሌሎች ክልሎችም የአማራ ክልልን አርአያነት በመከተል ለስፖርቱ እንዲሰሩ አሳስቧል። ለቼስ ስፖርት ወሳኝ የሆኑት ግብዓቶች በቀላሉ ሀገር ውስጥ አለመገኘታቸው እና ያለው የማዘውተሪያ ሥፍራ እጥረት አሁንም የስፖርቱ ማነቆዎች መሆናቸውን ግን አልሸሸጉም። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍም መንግሥትም ይሁን ባለሀብቱ ርብርብ እንዲያደርግም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በየቀኑ ለስድስት ሰዓታት ስልጠና የሚሰጠው ፤የወቅቱ ብቸኛው በሥራ ላይ ያለ ዓለም አቀፍ ዳኛ አቶ ደጀን ዘላለም ነው፡፡ በዚህ ስልጠና ላይ እየተሳተፉ ካሉ ዳኞች ውስጥ ጥቂቶቹ ልምድ ያላቸው ከፊሎቹ ደግሞ በቂ የውድድር ዕድል ያላገኙ መሆናቸውን ተገንዝቦ የአንደኛ ደረጃ የዳኝነት ስልጠናንም በማካተት ስልጠናው እየተሰጠ መሆኑን ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረገው ቆይታ ይናገራል።

በስልጠናው ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰቱ ችግሮችን ሳይሆን በመላ ዓለም የትኛውም ውድድር ላይ የሚታዩትን እንቅፋቶች በማንሳት በስፋት ውይይት እያደረጉ የመማር ማስተማር ሥራው እየተሳለጠ መሆኑን ነው የሚገልፀው። እንደዚህ ዓይነት የሙያ ማሻሻያ ስልጠናዎች በስፋት መስጠቱ በሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ የሚከሰቱ ስህተቶችን በማረም ስኬታማ ውድድር ለመምራት እንደሚያስችልም ነው የተናገረው፡፡

« የትኛውም ውድድር ደምቆ ከቅሬታ የጸዳ እንዲሆን ተከታታይነት ያላቸው ስልጠናዎች የወሰዱ ዳኞች መኖር የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል» ያለው ደጀን የዛሬዎቹ ሰልጣኞች ሙያቸውን ከማሻሻላቸው ባሻገር በሚኖሩበት ክልል ውስጥ ተተኪ ዳኞችን በማፍራት በኩልም ከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚሰጣቸውም ጠቁሟል፡፡ የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን እየሰጠ ያለውን ስልጠና ጥር 27 ቀን 2009.ም ይጠናቀቃል፡፡ ፌዴሬሽኑ ከነዚህ ሰልጣኞች ውስጥ አምስት ጠንካራ ዳኞችን በመምረጥ ለዓለም አቀፉ ቼስ ፌዴሬሽን ይልካል። በስልጠናው ማገባደጃ ላይ ሁሉም ሰልጣኝ ፈተና ይወስዳል። የተሻለ ውጤት ያስመዘገበም ለዓለም አቀፉ ቼስ ፌዴሬሽን ውጤቱ ይላክለታል፡፡ በመካከለኛ ውጤት ላይ የሚገኙት ደግሞ የሀገር ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ የዳኝነት እውቅና ይሰጣቸዋል፡፡ ዝቀተኛ ውጤት ያለው ካለ በሌላ ዙር በድጋሚ እንዲሳተፍ እንደሚደረግ አሰልጣኝ ደጀን በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን ከውድድሩ ጎን ለጎን በቅርቡ በጅማ ከተማ ለሚያካሂደው «የአፍሪካ ዞን 4 ነጥብ ውድድር ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። በዚህ ውድድር ላይ ግብጽን ጨምሮ 13 ሀገራት ተሳታፊ እንደሚሆኑም ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

ታምራት አበራ

Published in ስፖርት
Thursday, 02 February 2017 18:03

የእትዬ ሉሲ አገር

እትዬ ሉሲ ማናቸው? የሚል ጥያቄ ስለማይነሳ ቀጥ ብዬ ወደ ጉዳዬ ብገባ ይሻላል፡፡ እንዲያው ምን አልባት ሉሲ ማንናት የሚል ኢትዮጵያዊ ከተገኘም ጋሽ ኦባማን መጠየቅ ይችላል( በእጁ ነክቷታል ብዬ ነው)፡፡

ለማንኛውም እትዬ ሉሲ ከዛፍ ላይ ወድቃ ከመሞቷ በፊት አፈር ፈጭታ ውሃ ተራጭታ ያደገችው አፋር ክልል ነው፡፡ እናላችሁ ሰሞኑን በስራ አጋጣሚ አፋርን የማየት እድል አገኘሁ፡፡ ገና ወደ አፋር እንደምሄድ ሳውቅ ታላቅ ደስታ ተሰማኝ። የመጀመሪያው ደስታዬ አዲስ አበባ ላይ ሲያንዘፈዝፈኝ የነበረውን ብርድ እፎይ ለማለት ነው( በኋላ ግን ማሪኝ አዲስ አበባ ብያለሁ) ፡፡ ሌላኛው ደስታዬ ደግሞ የሰው ዘር መገኛ የሆነችውን አፋር ለማየት በመታደሌ ነው ፡፡

ጉዞ ወደ አፋር አድርጌ ሁሉንም ምኞቴን አሳካሁ፡፡ እስኪ ዘው ብለን አፋር ከመግባታችን በፊት እግረ መንገዳችንን መንገድ ላይም ያጋጠመኝን ነገር ላካፍላችሁ፡፡ መቼም በዚህ ዘመን የጉዞ ማስታወሻ መጻፍ ኋላ ቀር እየሆነ ስለመጣ አልፌ አልፌ ነው(እና ታዲያ ከአዲስ አበባ እስከ አፋር የሚረዝም ፅሑፍ ልትፅፍ ነበር እንዴ? የሚል ካለ ልክ ነው)፡፡

የጉዞ ማስታወሻ ኋላ ቀር ሆኗል ያልኩበት ምክንያት እንዲህ ነው፡፡ ድሮ ድሮ መንገድ በቅጡ ስላልተዘረጋ አንድን አካባቢ የሚያውቀው የተወሰነ ሰው ብቻ ነበር፡፡ ያ ሰው ላላዩት ሰዎች ይተርካል ማለት ነው፡፡ ዛሬ ግን እኔ በመኪና ሄድኩ ብዩ ላወራ ስል ሌላው በአውሮፕላን ቀድሞኝ እዚያው ይደርሳል፡፡ በእርግጥ ይሄ ይሁን እንጂ የጉዞ ማስታዎሻ የሚያመቸው ግን በመኪና መሬት ለመሬት በመሄድ ነው። በአውሮፕላን የሚሄድ ሰው ምንም ነገር ማየት አይችልም(ሰማይ ላይ መንደር የለ፣ እንሰሳት የለ፣ ጫካ የለ)፡፡ ችግሩ ይልቅ አውሮፕላን ሳይሆን ዛሬ ዛሬ የመኪና መንገድ በየመንደሩ ስለገባ ማንም ሰው የትኛውንም አካባቢ ማወቅ ይችላል። ያም ሆኖ ግን ሁሉም ሰው አገሪቱን ከጫፍ እስከጫፍ አያውቅምና የጉዞ ማስታዎሻ መጻፋችንን አናቆምም(ምነው ሁሉም ከጫፍ እስከ ጫፍ አውቀዋለሁ ባለና እኛ መጻፉን በተውነው)። ስለጉዞ ማስታዎሻ ያወራሁት እግረ መንገዴን ነው(ይሄ እግረ መንገዴን የምለው ነገር በዛ አይደል?)ኧረ ለመሆኑ ዋና ጉዳይህ ምን ሆኖ ነው አትሉኝም? ዋና ጉዳዬማ በአፋር ክልል የሚከበረውን የባህል ሳምንት ለመታደም ነው። ባህሉ ታዲያ ምን ይመስል ነበር?(እሱን ሌላ ጊዜ)። እስኪ መጀመሪያ እዚያ እንድረስ። ጉዟችን ከዚህ ይጀምራል፡፡

አርብ ጥር 19 ቀን ከጠዋቱ 120 ላይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል ትንሿ መኪናችን ( አይሩፍ ሲሏት ሰምቻለሁ) ፊቷን ወደ ስድስት ኪሎ አዙራ አራት ኪሎን አቋርጣ እንደምንም የትራፊክ ጭንቅንቁን ጨርሳ በቃሊቲ በኩል ከአዲስ አበባ ወጣች፡፡ብዙም ሳታቆየን የአዳማን ፈጣን መንገድ ተያያዘችው፡፡ በነገራችን ላይ የአዳማ ፈጣን መንገድ ላይ ዞሮብኝ ነበር፡፡ መንገዶች እርስ በእርስ ተቆላልፈው የማየው ጽሑፍ አንዴ መግቢያ አንዴ መውጫ ይላል፡፡ በዚህ መንገድ ላይ እኔ ሾፌር ብሆን ኖሮ ወደ አዳማ የሄድኩ መስሎኝ ተመልሼ ወደ አዲስ አበባ እገባ ነበር፡፡ ሹፌሩንና የመንገዱን አሰራር እያደነቅኩ አዳማ ከተማ ገባን፡፡

ከዚህ ቀጥሎ የማገኛቸውን ትንንሽ ከተሞች እንግዲህ በስም አላውቃቸውም፡ ፡እኔ ግን ጉዞ ስሔድ አንድ የተለመደ ዘዴ አለኝ፡፡ የማላውቀው ከተማ ሲሆን ቶሎ ብዬ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለበትን እፈልጋለሁ፡፡ሌላ ባንክ ከሆነ ግን እገሌ አካባቢ በማለት ሰፊ ያደርግብኛል(የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁሌም የሚተማመኑባት ባንክ የተባለው ጉዞ ጠቋሚ መሆኑን ጨምሮ ይመስለኛል)፡፡

ጎበዝ! በጨለማ እንዳንገባ ፈጠን ፈጠን እያልን። የመተሐራ ከተማን አልፈን ጥቂት እንደተጓዝን አፋር ክልል ውስጥ እንደገባን ከጎን ሲያወሩ ሰማሁ። እውነታቸው ይሆን እያልኩ በጥርጣሬ ሳሰላስል ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጎን የአፋር ክልል ሰንደቅ ዓላማ ታየኝ፡፡ ልክ አፋር መሆኑን ሳረጋግጥ ሙቀት ተሰማኝ( አፋር ሞቃት ነው ሲሉ ሰምቼ እኮ ነው)፡፡

የምር ግን አፋር ክልል ከገባን ጀምሮ የምናገኘሁ ሁሉ የተንጣለለ ሜዳና ቅጠላቸውን ያረገፉ ዛፎች ናቸው፡፡ ከየት እንደሚያመጡት አላውቅም በዚያ በረሃ ውስጥ ለምለም ዛፎችም ይታያሉ፡፡ አብዛኞቹ ዛፎች ግን ከመድረቃቸው የተነሳ ውሃ ቢያገኙም እንኳን የሚለመልሙ አይመስሉም፡፡ በእትዬ ሉሲ አገር እነዚህን ቅጠል የሌላቸው ዛፎች ሳይ አንድ ነገር ትዝ አለኝ (እርግጠኛ ነኝ ምን ትዝ እንዳለኝ ገብቷችኋል)፡፡ ባለፈው ሳይንቲስቶች ሉሲ የሞተችው ከዛፍ ላይ ወድቃ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ሳይንቲ ስቶችንም ብዙ ሰው ውሸታም ሲል አምቷቸዋል፡፡ እንደ እኔ እንደ እኔ ግን ተመራማሪዎቹ ልክ ይመስሉኛል፡፡ ሉሲ እነዚያ የደረቁ ዛፎች ላይ ከወጣች መውደቋ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

በዚህ ጉዞዬ ውስጥ ዝም ብዬ እንደ ተጓዥ ብቻ የሄድኩ እንዳይመስላችሁ። አንዳንድ ጊዜ እንደመመራመርም ይቃጣኛል(ምኞታዊ ምርምር እንበለው ይሆን)? የአዋሽ ፓርክ አካባቢ ስንደርስ በመኪናው መስኮት ግራና ቀኝ የተለያየ ዓይነት የዱር እንስሳት ውርውር እያሉ መንገድ ያቋርጣሉ። በቅርቡ አይቼ እንኳን ያረጋገጥኳቸው ሚዳቋ፣ ሰስ፣ ከርከሮ፣ ጅብ ሲሆኑ ስማቸውን የማላውቃቸው እንስሳትም ይታያሉ። እነዚህ የጠቀስኩላችሁ አንድ ወይም ሁለት ብቻ የሚታዩ ሲሆን የዝንጀሮዎች ነገር ግን አይወራ። አንዳንዶቹማ ጭራሽ መኪና ለማስቆምም የሚቃጣቸው ይመስላል። እነዚህ ዝንጀሮዎች በመኪና መስኮት የሚወረወርላቸውን የሚበላ ነገር ጥበቃ መንገድ ላይ እንደተኮለኮሉ ሉሲ ብታያቸው ኖሮ እንዲህ ትል ነበር። «ወይ ነዶ! የሰው ልጅ ከእኛ እንዳልተወለደ ሁሉ ዛሬ የኛ ዝርዮች ለማኝ የሰው ልጅ መጽዋች ይሁን? ወይ ጊዜ! እኛ ፍራፍሬ ለቀማ ዛፍ ለዛፍ(ከዛፍ ላይ ወድቀን እስከምንሞት ድረስ) ስንከራተት ኖረን የሰው ልጅ እንዲህ በመኪና አቧራ እያራገፈብን ይሂድእያለች ትበሳጭ ነበር።

የደረቁ ዛፎችን ባየሁ ቁጥር የሉሲን ነገር እያሰላሰልኩ የሙቀቱ ነገር እየባሰበት መጣ፡፡ በበረሃማው ሜዳ እየተጓዝን በዚህ ሰዓት እንገባለን በዚህ እንገባለን ክርክር ተጀመረ፡፡ እንደ እኔ ሰመራን የማያውቁት ፀጥ ብለው ያዳምጣሉ፡፡ ቶሎ እንደርሳለን የሚሉ ድምፆች ሲበዙ ደግሞ ሞራል ይሰማኛል፡፡

አዋሽ አርባ ስንደርስ ለምሳ ወረድን፡፡ ምሳ ከበላን በኋላ ሙቀቱ እየባሰበት መጣ(ስንት ጊዜ እየባሰበት አልኩ)። ወደ ሰመራ እየቀረብን በሔድን ቁጥር ጽሑፎች ሁሉ አፋር አፋር መሽተት ጀመሩ (የጽሑፍ ሽታ እንዴት አይነት ይሆን?) የግል ንግድ ቤቶች ስያሜ ዳሎል፣ ኤርታሌ፣አሳይታ፣ ከሰም፣ ተንዳሆ የሚል ይበዛባቸዋል(ስምን አካባቢ ያወጣዋል ነው እንግዲህ)፡፡

እነዚህ አካባቢዎች ቦታን ከማስተዋወቅ በተጨማሪ ንግድ ቤቶቹም እንደ አካባቢው የአየር ሁኔታ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ላይ «ሙቅ ሻወር አለ» እንደሚባለው ሁሉ እዚህ ቦታ ግን ግራና ቀኝ የሚታዩት ሻወር ቤቶች ሁሉም «ቀዝቃዛ ሻወር አለ» የሚሉ ናቸው። ምክንያቱም ሰው ወደ ሻወር ቤት የሚገባው ሰውነቱን ለመታጠብ ብቻ ሳይሆን ሰውነቱን ለማቀዝቀዝ ጭምር ነው፡፡

ከክልሉ ዋና ከተማ ሰመራ ለመግባት ጥቂት እንደቀረን በሰፊው የተንጣለለ ሜዳ ይታያል፡፡ በሜዳማ ቦታ ላይ ብዙ ጊዜ የሚታየው ጨፌ ወይም ለምለም ሳር ነበር፡፡ በዚህ በአፋር ሜዳ ላይ ግን ይህ አልሆነም፡፡ በሰፊው ሜዳ ላይ የሚታዩ ነጫጭ ፍየሎች ናቸው፡፡ ፍየሎቹን ከርቀት ያየ ሰው ሜዳው ላይ ፈንድሻ ፈሷል እንዴ? ብሎ ራሱን ይጠይቃል፡፡ ይህን የሚያስብለው ፍየሎቹ ከርቀት ትንንሽ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹ ነጫጭ መሆናቸው ነው፡፡ ከርቀት ሲታዩ ትልቅነታቸው የሚታወቀው ግመሎች ብቻ ናቸው(ግመል ሰርቆ አጎንብሶ የሚለው አባባል የገባኝ ያኔ ነው)፡፡

ሰመራ ከተማ ልንገባ ትንሽ ሲቀረን ሎጊያ ከምትባል ከተማ ደረስን፡፡ ሎጊያ የሰመራ ከተማ መግቢያ መሆኗን ሲነግሩኝ ‹‹ሎግ ኢን›› ብሎ በፌስቡክ ገብቶ አለምን እንደማየት ሆነብኝ፡፡ አሁን እንግዲህ «ሎግ ኢን» ብለን ወደ ሎጊያ ገብተናል፡፡ እትዬ ሉሲ አገር ሄጄ ገና ሰመራ ከተማ ከመድረሴ ‹‹አፋረንሲስ ካፌና ሬስቶራንት›› የሚል አነበብኩ፡፡ አፋረንሲስ የሉሲ ሳይንሳዊ ስም በመሆኑ አሁንም እሷው ትዝ አለችኝ፡፡

ሰመራ ከተማ ውስጥ የገቡበት ቤት ሁሉ ጣሪያው በቬንትሌተር ተተብትቦ ይታያል፡፡ እንዲያውም አንድ ቤት ውስጥ ከቬንትሌተሩ ፍጥነት የተነሳ ተነቅሎ ላዬ ላይ ይወድቃል ብዬ ተነሳሁ፡፡ በሰመራ ከተማ ውስጥ ሌላው የሚያስገርመው ነገር የሆቴል አልጋዎች ናቸው፡፡ ጎበዝ ይሄ ነገር ብዙ ስለሚያስወራ ሌላ ጊዜ ልመለስበትና አሁን ግን በሎጊያ በኩል ‹‹ሎግ አውት›› ብያለሁ፡፡

 

ዋለልኝ አየለ

Published in መዝናኛ

ብዙዎቻችን በልጅነታችን ምን መሆን እንደምንፈልግ ምኞት እናስቀምጣለን። በትምህርት ቤት ‹‹ምን መሆን ትፈልጋለህ?›› ስንባል የምንመኘውን እንናገራለን። አንዳንዱ በልጅነቱ የተመኘውን ሆኖ ይገኛል። አንዳንዱ ደግሞ በልጅነቱ የተመኘውን መሆን ባይሳካለትም ባልጠበቀው መስክ ተሰማርቶ ስኬታማ ይሆናል። በልጅነት የተመኙትን መሆንም፤ ያላሰቡትን መሆንም በብዙ ሰዎች ላይ የምናየው እውነታ ነው።

አንዳንዱ ደግሞ ምኞትን ከአጋጣሚ አደባልቆ ለስኬት መረማመጃ ያደርገዋል፡፡ አሁን የማስተዋውቃችሁ ወጣት ገና በልጅነቱ የተመኘውን እንዲሁም በኋላ የመጣለትን ፍላጎት ጨምሮ የሁለት ሙያ ባለቤት ሆኗል። ብዙዎቻችን ወጣቱን የምናወቀው በቴሌቭዥን «ኢንቲባራ» በሚለው የአፋርኛ ዘፈኑ ነው። ሰመራ ዩኒቨርሲቲ የተማሩ ሰዎች ደግሞ በጂኦሎጂ መምህርነቱ ያውቁት ይሆናል። ወጣቱ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርጎ ነበርና ያሲን ከድር ማነው? የሚለውን ከጽሁፉ እናገኛለን።

ትውልድና እድገት

ወጣት ያሲን ከድር ተወልዶ ያደገው በአፋር ክልል በረሃሌ አካባቢ ነው። እንደ አካባቢው ልጆች ፍየሎችና ግመሎች እያገደ አደገ። ከልጅነቱ ጀምሮ ሙዚቃ ይወዳል። መውደድ ብቻ ሳይሆን በቤት ውስጥ በእረኝነት ተልዕኮዎቹ ሁሉ ያንጎራጉራል። ሁኔታዎች በፈቀዱለት ሁሉ የሚያዳምጣቸውን ዘፋኞች ፈለግ በመከተል ዘፋኝ የመሆን ምኞት አደረበት። በበዓላትና ሕዝብ በሚሰባሰብባቸው ቦታዎች ሲዘፍን የሰሙት ሁሉ ካሴት ማውጣት እንደሚችል ይነግሩታል። ሕዝባዊ ዝግጅቶችና በዓላት ሲኖሩ ደግሞ እርሱን እንዲዘምር ይጠሩት ነበር። ወደ ትምህርት ቤት ከገባ በኋላም የትምህርት ቤቱ መምህራንና ጓደኞቹ ጥሩ ድምፅ እንዳለው ይነግሩታል።

ድምፃዊው ያሲን

ለሙዚቃ መጀመር ምክንያት የሆነው ትምህርት ቤት ነው። በወቅቱ እርሱና ባልንጀሮቹ የአካባቢያቸውን ባህላዊ ጨዋታ እንዲያሳዩ በመምህሮቻቸው ይታዘዛሉ። ከተማሪዎቹ ውስጥ ያሲን የአካባቢውን ባህላዊ ጨዋታዎች በሚገባ መጫወት ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ያሲንን ተወዳጅ እንዲሆን ያደረገው ደግሞ ግጥም መጻፉ ነበር። በትምህርት ቤቱ ውስጥ እንደ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት፣ ኤች አይ ቪ ኤድስና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ያቀርባል። በዚህ የተጀመረው የያሲን ገጣሚነት በኋላ የዘፈን ግጥም ወደመድረስ እያደገ መጣ፡፡

ግጥም ለመጻፍ ምክንያት የሆነው ሌላው ምክንያት ደግሞ የአረብኛ ጽሁፎችን ማንበብ መጀመሩ ነው። «ነሺዳ» የተባለውን የአረብኛ ጽሁፍ ካነበበ በኋላ የዘፈንም ሆነ የመድብል ግጥሞችን መጻፍ ጀመረ። በትምህርቱ እየገፋ ሲመጣ የግጥምና የድምጽ ችሎታውን በመረዳት ካሴት ማውጣት እንዳለበት አመነ። ተሳክቶለትም ዘፈኑ ለሕዝብ ደረሰ።

የሙዚቃ ስራውን ለሕዝብ ባደረሰ ሰሞን በሃይማኖት ምክንያት ብዙ ዘፋኞች ላይ እንደሚደርሰው በእርሱም ዘንድ የቤተሰብ አቀባበሉ ጥሩ አልነበረም። ምንም እንኳን አባቱ ግጥም በጣም የሚወዱ ቢሆንም ዘፋኝ እንዲሆን ግን አያበረታቱትም። እናቱና ሌሎች የጎረቤት ሰዎች ዘፋኝ መሆኑ በወቅቱ ቅር ቢያሰኛቸውም አሁን ግን ያ ባህል እየቀረ እንደሆነ ወጣት ያሲን ይናገራል።

ዘፋኝ መሆኑ ምን አስገኘለት?

ወጣት ያሲን ዘፈን በካሴትና በቪሲዲ ካወጣ ጊዜ ጀምሮ በቴሌቪዥን እንዲሁም በመድረክ መታወቅ ጀመረ። የተለያዩ የባህልና ሌሎች ሕዝባዊ በዓላት ሲዘጋጁ በተጋባዥነት ይጠራል። ስራዎቹንም ያቀርባል፡፡ በዚህም በብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘዋውሯል። ይህ ደግሞ የአገሩን ታሪክ፣ ባህልና ወግ ይበልጥ እንዲያውቅ አድርጎታል። እርሱ የአገሩን ታሪክ ሲያውቅ የአካባቢውን ባህልና ቋንቋ ደግሞ ለሌሎች አስተዋውቋል።

እንዲያውም አንድ ገጠመኙን ሲናገር «ባህርዳር እያለሁ አንድ በቴሌቭዥን የምታውቀኝ "አፋርን ያወቅኩት በአንተ ነው" ብላኛለች። የእኔን ዘፈን ከሰማች በኋላ አፋር የት ነው? ምንድነው? እያለች አገሩን ለማወቅ ጥረት አድርጋ እንደነበር ነግራኛለች። ብዙ ሰዎችም የአፋርኛ ቋንቋን ባይናገሩም ቋንቋውን እንዲያውቁ አድርጊያለሁ። የአካባቢዬ ባህልና ቋንቋ በእኔ ሲታወቅ ደግሞ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል» ይላል።

የአካባቢውን ባህል ያስተዋወቀው በዘፈን ብቻ አይደለም። በግጥሞችና በሌሎች የስነ ጽሁፍ ስራዎችን መድረክ ላይ እየተገኘ ያቀርባል። በአካባቢው ላሉና ተሰጥኦ ላላቸው ወጣቶቸም ልምዱን በማካፈል ችሎታቸውን እንዲጠቀሙበት ያስተምራቸዋል። ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመሆንም የሚያስፈልጋቸውን የባህል መሳሪያም ሆነ የአልባሳት ዕቃዎች ሙያዊ እገዛ ያደርግላቸዋል። ወጣቶቹ የእርሱን አርአያነት እንዲከተሉ ያደረጋቸው ደግሞ እርሱ ከልጅነቱ ጀምሮ ያስበው የነበረውን ሙያ ሆኖ በማየታቸው ነው። ዘፋኝ መሆኑ አገሩን እንዲያውቅ ከማድረጉ በተጨማሪ ለሌሎችም አርአያ ለመሆን አስችሎታል።

መምህሩ ያሲን

ዘፋኝ መሆን የልጅነት ምኞቱ ነበር። በኋላ ግን ራሱን በመምህርነት ሙያ ውስጥም አገኘው። ወጣቱ በ2001 .ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ በስነ ምድር ጥናት (ጂኦሎጂ) ተመረቀ። እንደተማረ «አላማ» የተባለ የማዕድን ቁፋሮ ድርጅት ውስጥ መስራት ጀመረ። በዚሁ በማዕድን ቁፋሮ ድርጅት ውስጥ እያለ ጂኦሎጂስት የመሆን ፍላጎቱ እያደገ መጣ። ይህንን ፍላጎቱን ደግሞ ማሳካት የሚችለው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመግባት እንደሆነ አመነ። በመሆኑም ከ2007 .ም ጀምሮ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ጂኦሎጂ ማስተማር ጀመረ።

ዘፋኝነት ከመምህርነት

ያሲን የሚያስተምራቸው ተማሪዎች በቴሌቪዥን ሲዘፍን ያውቁታል። ይህ ግን በመምህርነቱ ላይ ምንም ያመጣበት ተፅዕኖ የለም። «መድረክ ላይ ስወጣ ዘፋኝ ነኝ፤ ክፍል ውስጥ ስገባ መምህር ነኝ» የሚለው ያሲን፤ ክፍል ውስጥ ሲገባ የሚያተኩረው በትምህርቱ ላይ ብቻ ነው። «ተማሪዎቹ ክፍል ውስጥ ስገባ በጣም ነው የሚያከብሩኝ። ይህ የሆነው ደግሞ በደንብ ስለማስተምራቸው ነው። ትምህርቱን በጣም ስለምወደው በሚገባ ተዘጋጅቼ ነው የምገባው። ተማሪዎች በምሰጣቸው ትምህርት ደስተኛ ስለሚሆኑ እኔን በዘፈን ክሊፕ ማየታቸው ክፍል ውስጥ ምንም ያመጣው ተፅዕኖ የለም» የሚለው ያሲን፤ ማስተማር ከመውደዱ የተነሳ የተመደበበትን የጂኦሎጂ ትምህርት ብቻ ሳይሆን የአፋርኛ ቋንቋም አልፎ አልፎ እንደሚያስተምር ይናገራል።

የወጣቱ ራዕይ

ወጣቱ በሁለቱም ሙያው ስኬታማ መሆን ይፈልጋል። በመምህርነቱ ሙያ በጂኦሎጂ የምርምር ስራዎችን መስራት ይፈልጋል። ከጂኦሎጂ በተጨማሪ ደግሞ በአመራርነትም ሌሎች ጥናቶችን ለመስራት በዝግጅት ላይ ይገኛል። በአመራርነት (ሊደርሺፕ) 2008 .ም ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ትምህርቱን ተቀብሏል።

በዘፋኝነቱ ደግሞ በቀጣይ በሌሎች ቋንቋዎች የአገሩን ባህልና ወግ ማስተዋወቅ ይፈልጋል። «የዘፋኝነት ስራዬን የምሰራው ለገንዘብ አይደለም» የሚለው ወጣት ያሲን፤ የኪነ ጥበብ ስራ አንዴ ውስጡ ከገቡ ለመውጣት አስቸጋሪ እንደሆነ ይናoገራል። የኪነ ጥበብ ስራ በውስጣዊ ጥልቅ ስሜት የሚሰራ ስለሆነ መተው እንደማይችልና በዘፋኝነቱም በመምህርነቱም በመቀጠል በሁለቱም ስኬታማ ሰው መሆን የመምህርና ድምፃዊ ያሲን ምኞት ነው። ምኞት ብቻም ሳይሆን በሁለቱም በኩል ስኬታማ መሆኑን አሳይቷል። ይህ የስኬት ቁርጠኝነት ለብዙ ወጣቶች አርአያ የሚሆን ነው።

 

ዋለልኝ አየለ

Published in ማህበራዊ

   

ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል አንዱ የሆኑት                                             የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋሙ ምክረ ሃሳብ ፤

የአቶ በላይ ተረፈ የግብር ክፍያ ማስረጃ፤

 

 

አቶ በላይ ተረፈ ይባላሉ፤ ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ነው፡፡ ምንም እንኳ ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተወለዱ ቢሆኑም በንግድ ስራ ተሰማርተው ውጤታማ መሆን ችለዋል፡፡ ሃብት ማፍራት ሲጀምሩም በአካቢው በተፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት እድል በመጠቀም በ1993 .200 ሄክታር መሬት ከዞኑ ኢንቨስትመንት ቢሮ በህጋዊ መንገድ በመረከብ የስራ ዘርፋቸውን ይቀይራሉ፡፡

እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ መሬቱን ለማልማትና ምርት ለማግኘት ከሶስት አመት ያላነሰ ጊዜ ወስዶባቸዋል፡፡ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይም ጠይቋቸዋል፡፡ ወደ ልማት ከገቡ በኋላ ግን መሬቱ ከጠበቁት በላይ ምርት መስጠት ቻለ፡፡ በየአመቱም እንደ በቆሎ፣ ሰሊጥና ሌሎችንም የቅባት እህሎች በማምረት አመርቂ ገቢ ማግኘት ከመቻላቸውም ባሻገር ለ200 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡ ለመንግስትም ቢሆን በየአመቱ የሚጠበ ቅባቸውን የመሬት፥ የምርት ትርፍና የሰራተኛ ግብር በመክፈላቸው በተለያዩ የክልሉ ቢሮዎች ምርጥ አርሶ አደር በመባል ለሽልማት በቅተዋል፡፡

ባለሃብቱ ልማታቸውን ለማስፋፋትና ምርታቸውን በቀጥታ ወደ ውጭ ለመላክ አቅደው ዝግጅት እያደረጉ ባሉበት ወቅት ግን ያልጠበቁት አስደንጋጭ ዜና መስማታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ «1999 .ም በፊንጫ አመርቲነሽ ፕሮጀክት አማካይነት ከአካባቢ ያቸው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችን ለማስፈር የሚውል መሬት ተፈልጎ በመታጣቱ እኔን ጨምሮ 13 ኢንቨስተሮች ከመሬታችን ልንነሳ መሆኑን ስሰማ ማመን አቅቶኝ ነበር» ይላሉ፡፡ አክለውም «በዛው ዓመትም መሬቱ በድብቅ ተላልፎ መሰጠቱን ሰምተናል» በማለት ይናገራሉ፡፡

ስለጉዳዩ የሰሙት ግን ከአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ከአንድም የመንግስት አካል ሳይነሳና ለእነርሱም ምንም ሳይነገራቸው ለተከታታይ ሶስት ዓመታት ማልማት መቀጠላቸውን ይናገራሉ፡፡ በ2002 .ም ግን የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ያለምንም ማስጠንቀቂያ መሬቱ ለልማት ስለሚፈለግ መነሳት እንዳለባቸው፤ በምትኩም በአማራ ክልል ጎጃም ድንበር አገምሳ አካባቢ መሬት እንደሚሰጣቸው እንደተገለፀላቸው ያብራራሉ፡፡ ይሁንና የተመሩት መሬት ለመስኖ የሚውል ውሃ የሌለበት፥ የመጠጥ ውሃ እንኳ ለማግኘት አምስት ሰዓታት መጓዝ የሚጠይቅ፥ ያልለማና አካባቢውም ለደህንነታቸው የሚያሰጋ በመሆኑ ሌላ ተመጣጣኝ የሆነ መሬት እንዲሰጣቸው ለዞኑ ኢንቨስትመንት ቢሮ መጠየቃቸውን ያመለክታሉ፡፡ የእርሳቸውና የሌሎቹ ባለሃብቶች ጥያቄ ግን በፅህፈት ቤቱ ተቀባይነት አለማግኘቱን፤ ይልቁንም በወቅቱ የነበሩ አመራሮች እልህ በመጋባት ምንም አይነት መሬት እንደማይሰጣቸው የገለፀላቸው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

2002 .ም ለ13 ኢንቨስተሮች በውሉ መሰረት ስላልሰራችሁ በአስቸኳይ ከመሬቱ መነሳት አለባችሁ የሚል ደብዳቤ የተሰጣቸው ሲሆን፤ ውላቸውም እንዲፈርስ መደረጉን ይጠቁማሉ፡፡ ይሁንና ከ13ቱ ባለሃብቶች መካከል ለአራቱ ምትክ መሬት እንዲያገኙ መደረጉን ጠቅሰው፤ «ለእነዚህ ባለሃብቶች የሰጠቿው በወቅቱ ከነበሩ አመራሮች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ እንጂ ምንም አይነት ህጋዊ አግባብ ተከትለው አይደለም፤ ይህም በአንድ ኢፍትሃዊ የሆነ የአስተዳደር ችግር ነው» ይላሉ፡፡

«ብዙ አልሜ ያለኝን ጥሪት ሁሉ ያፈሰስኩበት ኢንቨስትመንት ያለምንም ካሳ ሜዳ ላይ መቅረቱ እጅግ ልቤን ሰብሮታል» የሚሉት ደግሞ ሌላው ኢንቨስተር አቶ አሸናፊ ለገሰ ናቸው፡፡ እርሳቸውም 200 ሄክታር መሬት በ1993 .ም ከዞኑ ኢንቨስትመንት ቢሮ ወስደው በአመት ከ10 እስከ 15ሺ ኩንታል በቆሎና ከሁለት ሺ ኩንታል ያላነሰ ሰሊጥ ያመርቱ እንደነበር ይገልፃሉ፡፡

ሌሎችንም ሰብሎች ጨምሮ ከ21ሺ ኩንታል ምርት ይሰበስቡ እንደነበርም የሚያስታውሱት አቶ አሸናፊ፤ በዚህም በድምሩ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ያገኙ እንደነበር ያወሳሉ። ውላቸው እስከተቋረጠበት እስከ 2002 .ም ድረስም ለመንግስትም የሚገባውን ግብር በአግባቡና ሳያቋርጡ መክፈላቸውን ያመለክታሉ፡፡ በግብርና ስራቸው ከ200 እስከ 250 ለሚደርሱ የአካባቢው ነዋሪዎች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ እድል መፍጠር ችለው ነበር፡፡

እንደ ማንኛውም ዜጋ በልማት ምክንያት ሃብት ካፈሩበት መሬት መነሳታቸውን እንደማይቃወሙ የሚናገሩት አቶ አሸናፊ፤ አግባብነት በሌለው መንገድ ግን «በውሉ መሰረት አልሰራችሁም» በሚል ሰበብ እንዳያለሙ መደረጉና ላፈሩትም ሃብትና ንብረት ካሳ አለመከፈሉ የኢንቨስትመንት ህጉን የሚፃረር መሆኑን ነው የሚያስረዱት፡፡ «ከቦታው ያለምንም ማስጠንቀቂያና ንግግር ነው የተነሳነው። መሰረት በሌለው ተጨባጭ ምክንያት እንድንነሳ መደረጉ ህጉን የሚፃረር ትልቅ አስተዳደራዊ በደል ነው። ከቦታው ከተነሳው ውስጥ ለአራቱ መስጠታቸው አሰራራቸው ፍትሃዊ አለመሆኑን ትልቅ ማሳያ ነው» ሲሉም ነው ያብራሩት፡፡

የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ይህንን ሲወስን የወረዳው ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ከባለሃብቱ ጎን ቆሞ እስከመጨረሻው ድረስ ሲከራከርላቸው እንደነበር፤ ይሁንና ከዞኑ ሃላፊዎች በተፃፈ ማስጠንቀቂያ ውሳኔውን ተቀብለው ለመፈፀም መገደዳቸውን ነው ያመለከቱት፡፡ ይህንኑ ጉዳይ ለክልሉ እምባ ጠባቂ ተቋም አቤት ብለውም የተወሰነው ውሳኔም ሆነ ድርጊት አግባብ አለመሆኑን ማጠራቱንም ጠቁመዋል፡፡

ግለሰቡ በደረሰባቸው በደል ያፈሩትን ሃብት ጥለው ከመውጣታቸውም ባሻገር የሚያስተዳድሯቸው ቤተሰቦቻቸውን ለመበተን ተገደዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የእለት ጉርሳቸው ለመሸፈን ሲሉ ተባራሪ ስራ በየተቋማቱ እየተዘዋወሩ እንደሚሰሩ አስረድተዋል፡፡

ባለሃብቶቹ ለዝግጅት ክፍሉ ባቀረቡት የሰነድ ማስረጃ መሰረትም የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት በ1999.ም ቦታው ለፊንጫ አመርቲነሽ ፕሮጀክት ማስፋፊያ ተላልፎ መሰጠቱን ያሳያል፡፡ በ08/11/02 .ም ደግሞ 13ቱም ባለሃብቶች እርሻውን ሜካናይዝድ ስላላደረጉ ወረዳው እንዲያስነሳቸው የፃፈው ደብዳቤ ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ማለትም በ6/11/02 ላይ ለአራቱ ባለሃብቶች ብቻ ምትክ መሬት እንዲሰጣቸው ትእዛዝ ያስተላለፈበት ደብዳቤ በእጃችን ገብቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጋዜጣው ለእትም እስከቀረበበት እለት ምትክ መሬት ካልተሰጣ ቸውና ካሳ ካልተከፈላቸው ዘጠኝ ኢንቨስተሮች መካከል ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዘላቸውም ለዝግጅት ክፍላችን በስልክና በአካል አቤቱታቸውን ማቅረብ ቀጥለዋል፡፡ እኛም አቤቱታቸውን ይዘን በቅድሚያ ለጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ሃሎ ብለናል፡፡ ሃላፊው አቶ ስመኘው አሊም «እኔ ወደቦታው የመጣሁት በቅርቡ ነው፤ቢሮው የተቋቋመው ከ2002 .ም በኋላ በመሆኑ የምሰጠው መረጃ በሰነድ መልክ የተቀመጠውን ብቻ ነው» ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ስመኘው ገለፃ፤ ባለው ማስረጃ መሰረት ባለሃብቶቹ ከቦታቸው የተነሱት የዞኑ ኢንቨስትመንት ኮሚቴ ባደረገው ማጣራት በውሉ መሰረት ሜካናይዝድ ባለማድረጋቸው ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ለክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አመልክቶ ለወረዳውም በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት በ2003 .ም እንዲነሱ አድርጓል፡፡ በወቅቱ መሬቱንም ወደ ክልሉ መሬት ባንክ እንዲገባ ነው እንጂ የተደረገው ለማንም አካል ተላልፎ አልሰጠም፡፡ ባለሃብቶቹ ከመነሳታቸው በፊት ግን ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን መረጃዎቹ ያመለክታሉ፡፡

«ባለሃብቶቹ ግን አስፈላጊውን ግብር ሁሉ መክፈላቸውን አረጋግጠናል» የሚሉት አቶ ስመኘው፤ ለአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል መፍጠራቸውም የሚታወቅ ቢሆንም ወረዳው ከበላይ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ውሳኔውን ማስፈፀሙን ነው ያስረዱት፡፡ «ባለሃብቶቹ በተለያዩ የክልሉ ቢሮዎች ምርጥ አርሶ አደር ተብለው ተሸልመው ባለበት ሁኔታ ሜካናይዝድ አላደረጋችሁም በሚል ሰበብ ውላቸውን መሰረዙ የሚጣረስ አይደለምየእኛ ጥያቄ ነበር፡፡ አቶ ስመኘውም «እነርሱ ምርጥ አርሶ አደር ተብለው ስለመሸለማቸው የማውቀው ነገር የለም፤ እኛ የምናውቀው ውሉን ሰርዙ ስንባል መሰረዛችንን ብቻ ነው» በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ባለሃብቶቹ እንደሚሉት ውላቸው የተሰረዘውና መሬቱን እንዲለቁ የተደረገው ህጋዊ ማስረጃ ይዘው ከሆነ መከራከር እንደሚችሉ ይመክራሉ፡፡ በሌላ በኩልም ከተነሱት መካከል ለከፊሎቹ መሰጠቱ በራሱ ተገቢ አለመሆኑን እርሳቸው ያምናሉ፡፡

«ባለሃብቶቹ ከመሬቱ እንዲነሱ የተደረጉት ለፊንጫ አመርቲነሽ ማስፋፊያ ሳይሆን በውሉ መሰረት ሜካናይዝድ ባለማድረጋቸው ለአካባቢው ህብረተሰብ የስራ እድል ባለመፍጠራቸውና የሰራተኛ ግብር ባለመ ክፈላቸው ነው» ያሉት ደግሞ የሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዱኛ ዘውዴ ናቸው፡፡ ይህም በተደረገው ማጣራት መረጋገጡንና ለባለሃብቶቹም በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ነው፡፡

ይሁንና በውሉ መሰረት አልሰሩም ተብለው ከተነሱት ዘጠኝ ባለሃብቶች መካከል ለአንዱ ግለሰብ ምትክ መሬት እንዲሰጥ መደረጉን ያምናሉ፡፡ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዱም «በተደረገው ምርመራ በግለሰቡ ላይ የቀረበው ማስረጃ ትክክል አለመሆኑ በመጣራቱ ነው፤ ሌሎቹም ቢሆን አላግባብ መብታቸው ተጥሶ ከሆነ ዳግም ጉዳያቸው እንዲታይላቸው ጥያቄ ማቅረብ ይችላሉ» በማለት ምላሽ ሰጠተዋል፡፡

የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የድጋፍና ክትትል ቡድን መሪ አቶ በላይ ዱፌራ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ማንኛውም ባለሃብት መዋዕለ ንዋዩን ከማፍሰሱ በፊት አስገዳጅ ውል መፈረም ይጠበቅበታል፡፡ ይህንን ስምምነት በአግባቡ ካልፈፀመና በድጋፍና በማስጠንቀቂያ ካልተሻሻለ መሬቱን የሚቀማ ስለመሆኑ በውሉ ተደንግጓል፡፡ ባለሃብቶቹ የተነሱትም በዚሁ አግባብ ሲሆን ከመነሳታቸው በፊት አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ተደርጓል፤ በውሉ መሰረትም እንዲሰሩ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ያሉ አመራሮችና የክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርድ ድረስ በመምከር ጉዳዩን መርምሮ በ2003 .ም ውላቸው እንዲቋረጥና መሬቱ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ተደርጓል፡፡

እርሳቸው ይህንን ቢሉም ባለሃብቶቹ ባመጡት ማስረጃ መሰረት በ2001 .ም የፊንጫ አመርቲነሽ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ባለሃብቶቹ ስራውን አላሰራ ስላሉት የዞኑ አስተዳደር ለጉዳዩ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ የሚያሳስብ ደብዳቤ ፅፏል፡፡ ይህም የባላሃብቶቹ ውል ከመሰረዙ በፊት ቦታው ለሌላ አካል ተላልፎ መሰጠቱን ያሳያል፡፡

ይህን አስመልከተው የቡድን መሪው «ውል ሳይቋረጥ መሬታቸው ተወስዶ ከሆነ ከህግ ውጭ በመሆኑ ምትክ መሬት ሊሰጣቸው ወይም መሬታቸው ተመላሽ ሊሆን ይገባል፡፡ ይሁንና የእነዚህ መረጃው እንደሚያመለክተው ውላቸው ቀድሞ መቋረጡን ነው» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

«13ቱ ባለሃብቶች ውስጥ አራቱ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ጉዳያቸው በድጋሚ ሲመረመር በተገኘው ውጤት የቀረበባቸው ማስረጃ ተገቢ አለመሆኑን ታውቆ መሬታቸው እንዲመለስላቸው ተደርጓል» የሚሉት አቶ በላይ፤ «በቅርቡ ደግሞ ለአንደኛው ባለሃብት መሬት ተሰጥቷል» ይላሉ፡፡ ቀሪዎቹ ባለሃብቶች ግን ውላቸው እስከሚቋረጥበት ጊዜ ድረስ በበሬ በማረሳቸው፣ የሰራተኛ ግብር ባለመክፈላቸው፥ የስራ እድል ከመፍጠር ይልቅም መሬቱን ለሌላ አካል አሳልፈው በመስጠታቸው ውሳኔው እንዲፀናባቸው መደረጉን ነው ያብራሩት፡፡

ባለሃብቱ አቶ በላይ ተረፈ ግን ሃላፊዎቹ በሚያቀርቡት ምክንያት አይስማሙም፡፡ «በአካባቢያችን መሰረተ ልማት ባለመሟ ላቱና ትልቅ ወንዝ በመኖሩ ያንን አልፎ ትራክተር መምጣት እንደማይችል ይታወቃል፡፡ በውሉ በግልፅ እንደተቀመጠው መሰረተ ልማት መስራት የሚገባው ውል ሰጪው የመንግስት አካል በመሆኑ በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው እገዛ እንዲያደርጉልን ብንጠይቅም በጎ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም» ይላሉ፡፡ የስራ ግብር አልከፈሉም በሚል የቀረበባቸውንም ክስም ትክክል አለመሆኑን በማስረጃ አስደግፈው ተናግረዋል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ከመሬቱ እስከሚነሱ ድረስ አንድም አካል በውሉ መሰረት አልሰራችሁም በሚል ክስ አለማቅረቡን ነው ያስረዱት፡፡

በኢፌዴሪ የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ መርማሪ አቶ ሽፈራው ቦጋለ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ተቋሙ የምርመራ ቡድን ቦታው ድረስ ልኮ ባጣራው መሰረት የዞኑ ኢን ቨስትመንት ጽህፈት ቤት ባለሃብቶቹ ከመሬቱ እንዲነሱ ያደረገው ውሉ ከመሰረዙ ከሶስት አመት በፊት ነው፡፡ ኮሚሽኑም ሆነ ሁሉም የክልሉ ሃላፊዎች ባላሃብቶቹ በውሉ መሰረት አልሰሩም ከተባሉበት አንዱ ምክንያት በዘመናዊ መንገድ አላረሱም የሚለውን ነጥብ ትክክል ነው፡፡ ይሁንና አስፈላጊውን መሰረተ ልማት ባልተዘረጋበትና ምንም አይነት ድጋፍ ባልተደረገበት ሁኔታ ባለሃብቶቹን ማስነሳታቸው ከልማታዊ አስተዳደር የሚጠበቅ አይደለም፡፡

«ግብር አልከፈሉም፤ ለአካባቢው ነዋሪዎችም የስራ እድል አልፈጠሩም ተብሎ የተነሳውም ሃሳብ ፈፅሞ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ያገኘነው የሰነድ ማስረጃም የሚያረጋግጥልን ይሄ ነው» የሚሉት አቶ ሽፈራው በተለይም የወረዳውና የዞኑ ሃላፊዎች ባካሄዱት ስብሰባ ላይ ባለሃብቶቹ ማልማታቸውን ለመንግስት የሚያስፈልገውን ግብር መክፈላቸውን የሚያስረዳ ቃለጉባኤ መኖሩን እንዳረጋ ገጠላቸው ያስረዳሉ፡፡

እንደ እርሳቸው እምነት፤ የተነሱት ምክንያቶች እውነት ናቸው ተብሎ ከታመነ ደግሞ ከ13ቱ ባለሃብቶች ውስጥ አስቀድመው ለአራቱ በቅርቡ ደግሞ ለአንዱ ብቻ ምትክ መሬት መስጠታቸው የፍትሃዊነት ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ ከዚያ ይልቅም በተለይም የቀድሞ የዞኑ አመራር ከጥቅም ጋር የተሳሰረ ውሳኔ መስጠታቸውን የሚያመላክት ነው፡፡ የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም የተፈጠረውን አስተዳደራዊ በደል መርምሮ ውሳኔ ከመስጠት ይልቅ ለተፈጠረው ስህተት ሽፋን እያደረገ መሆኑን ያመላክታል፡፡

«ኮሚሽናችን ባጣራው መሰረት አቤት ባዮች ውሉ የተቋረጠበት አግባብ በተመለከተ የዞኑ አስተዳደርና የዞኑ ኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት ምክንያት በመፍጠር ከህግ አግባብ ውጪ ውላቸው እንዲቋረጥ ለኮሚሽኑ በፃፉት ደብዳቤ አረጋግጧል» ይላሉ፡፡ የተጠቀሰው ምክንያትም ውልን ለማቋረጥ መነሻ ቢሆንም ውላቸው ግን የተቋረጠው በተባለው ምክንያት አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ይዞታው ለአመርቲነሽ ፕሮጀክት የሰፈራ መርሃ ግብር ትግበራ ማስፈፀሚያ እንደሆነ በምርመራቸው መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

ይህም የአቤት ባዮች ይዞታ ለተሻለ ልማት ተፈልጎ እንዲነሱ በመደረጋቸው በህገመንግስት አንቀፅ 40ና በአዋጅ ቁጥር 455/97 እንዲሁም ደንብ ቁጥር 135/99 መሰረት ከይዞታቸው ሲነሱና ሲፈናቀሉ ለንብረታቸው የካሳ ግምትና ምትክ መሬት የማግኘት መብታቸው ሊጠበቅላቸው ይገባል በማለት ተቋሙ የመፍትሄ ሀሳብ በ12/03/09 ለኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፤ ለሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አስተዳደር፤ ለሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት እንዲሁም ለጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ አስተዳደር ማቅረቡን ነው ያብራሩት፡፡ ይሁንና ተቋሙ በህግ የተሰጠውን የህዝብ እምባ የማበስ ተግባር በሁሉም አካላት ተቀባይነት አለማግኘቱ ምክረሃሳቡን ተቀብለው ለመተግበር እስካሁን ፍላጎት አለማሳየታቸውን ነው የጠቆሙት፡፡

የእምባ ጠባቂ ተቋሙ ይህንን ቢልም ከክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጀምሮ እስከወረዳ ያሉ የሚመለከታቸው አካላት የቀረበላቸው ምክረሃሳብ አለመኖሩን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡ ጋዜጣው የሁሉም አካላት ድምጽ በሚዛናዊነት እንዲሰማ አድርጓል። የባለሃብቶቹ ጥያቄ ሊመለስ እንደሚገባ ያምናል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ አለማግ ኘታቸውም በየአካባቢው አኩራፊ የህብረተሰብ ክፍል እንዲፈጠር እያደረገ በመሆኑም የክልሉ አመራሮች ጉዳዩን በአግባቡ ሊፈትሹት እንደሚገባም ጭምር፡፡

 

ማህሌት አብዱል

 

 

Published in ፖለቲካ

ከበዙት የልጅነት ትውስታዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በዚያን ዘመን በበርካቶች ትዝታ ውስጥ የነጭ እና ጥቁር ቴሌቪዥን ብልጫውን ይወስዳል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ሴኔጋል ከግብፅ እስከ ኬኒያ በአገርኛ አልባሳታቸው የደመቁ አፍሪካዊ ድምፃውያን በቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው በአፍሪካዊ ለዛ ይውረገረጋሉ፡፡

አፍሪካውያን ተሳታፊዎች ወራት ቆጥረው ለአህጉራዊ ስብሰባ ወደ መዲናቸው ጎራ ሲሉ እነዚህን ሙዚቃዎች በየተራ መኮምኮሙ የተለመደ ነበር፡፡ በዚያን ሰሞን ድምፃውያኑ በቴሌቪዥኑ መስኮት በተደጋጋሚ ከመከሰታቸው የተነሳም ዜማዎቹን ከሕብረቱ ጉባኤ ነጣጥሎ መመልከት ይከብድ ነበር፡፡ እነዚህ የዘመን ትዝታዎች ትውስታቸው ጥልቅ ነው፡፡

የአፍሪካ ህብረት ካሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ አንስቶ ሲያካሂድ የሰነበተው የህብረቱ 28ኛ መደበኛ ጉባኤ ከትናንት በስቲያ ተጠናቋል፡፡ ጉባኤው በተካሄደ ቁጥር ያለፈውን መለስ ብሎ ለማስታወስ ዕድል ይሰጣል፡፡ ነገር ግን ባለፈውና በአሁኑ ዘመን መካከል ያለው ልዩነት ነጭና ጥቁሩን ወደ ባለቀለም ቴሌቪዥን መቀየር ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁኑም አዲስ አበባ ከተማ ከዓመታት በፊት የነበራት የማይመስጥ ገፅታም ዛሬ ፍፁም የተለወጠ መሆኑም እንጂ፡፡

ብዙም ሳንርቅ ስምንቱን የተሳትፎ ዓመታት ሸርፈን በምልሰት እንመልከት፡፡ ከተማዋን በሁለት አቅጣጫዎች ገምሶ የሚያልፈው የቀላል ባቡር ፕሮጀክት አልታሰበም ነበር፡፡ በተለያዩ ክፍሎች ተንጣልለው የሚታዩት የጋራ መኖሪያ ቤቶችም ቢሆኑ እንደዛሬው አልተበራከቱም፡፡ እንዲያውም ከእነርሱ ይልቅ ያረጁ መንደሮች ብልጫውን ይይዛሉ፡፡ ወደ ሕብረቱ ዋና ፅሕፈት ቤት ብንመለከትም ትዝታው በኋላ ቀርነት ግርዶሽ የተሞላ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ስፍራው ላይ በቻይና ድጋፍ ሰማይ ጠቀስ ህንፃ ከመንጣለሉ በፊት እንደ አብዛኞቹ የከተማዋ ክፍሎች የማይማርክ ገፅታው ይጎላ ነበር፡፡

አዲስ አበባ በርካታ ትዝታዎቿን የኋሊት እየተወች ከሕብረቱ ምስረታ ዕድሜ ጋር ዕድገቷን ሽቅብ እያሰላች ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡ ከተማዋ እንደ መፅሐፍ ስትገለጥ ብዙ ትናንቶችን በውስጧ ከትባለች፡፡ የበርካታ አፍሪካውያንም የትዝታ ማሕደር ነች፡፡ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ጥያቄ ልቆ ሄዶ የባርነትን ካባ አውልቀው እስኪጥሉ ብርታታቸው ነበረች፡፡ አሁን ደግሞ የአህጉሩ ልጆች ከዚያ ዘመን የመብትና የነፃነት ጥያቄ ወጥተው የልማት ትብብራቸው ላይ ይገኛሉ፡፡ የዚህ ፍላጎት ማንፀባረቂያ መድረክም አዲስ አበባ ናት፡፡

ከትናንት በስትያ የሕብረቱ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ተገኝቼ ‹‹ከጉባኤው ቁምነገር በተጓዳኝ የአዲስ አበባ አክራሞታችሁ እንዴት ነበር?›› ያልኳቸው ነበሩ፡፡ በእርግጥ የእንግዶች ምልከታ ለየቅል ነው፡፡ ከፊሉ በከተማዋ አየር ፀባይ ሲደመም ሌላው በበኩሉ ፈጣን ልማቷ ያስደንቀዋል፡፡ ጆሴፍ ሌዮኔል ሳኮ የአንጎላ የግብርና ሚኒስትር ልዩ አማካሪ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ለሕብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ የነበራቸው ቆይታ አስደሳች ነበር፡፡

ከተማዋን በተመለከተ ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ትዝታ መነሻ በማድረግ ‹‹አዲስ አበባ በከፍተኛ የዕድገትና የልማት ጉዞ ውስጥ ትገኛለች›› ይላሉ፡፡ በተለይም የከተማው መስፋፋት፣ የአዳዲስ ህንፃዎች መበራከት እንዲሁም በዋናነት የቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የግርምታቸው ምክንያት ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻገር የከተማዋ አየር ፀባይ ሁሌም ወደ ኢትዮጵያ ጎራ ሲሉ የሚደመሙበት መሆኑንም አያይዘው ይጠቅሳሉ፡፡

ከቡርኪናፋሶ የመጡት ማሃዋ ካፓ ዊለር በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የስርዓተ ፆታ ልማት ዳሬክተር በመሆን አገልግለዋል፡፡ በስራቸው ምክንያት ባለፈው አንድ ዓመት አብዝተው ጎራ የሚሉባት አዲስ አበባ የቤታቸው ያህል ስሜት እንደፈጠረላቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይና ተወዳጅ ናቸው›› በማለት አስተያየታቸውን የሚሰጡት ካፓ ዊለር፤ በሕብረቱ ጉባኤ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አጋጣሚዎችም ጎራ የሚሉ ወዳጆቻቸው ይሄን አስተያየት እንደሚሰነዝሩ ይገልጻሉ፡፡ አዲስ አበባም እንግዶቿን የመቀበልና የማስተናገድ አቅሟ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ዘመናዊ እየሆነና እያደገ መምጣቱን ያብራራሉ፡፡

እንዲህ ያሉትን አለም አቀፍና አህጉራዊ ጉባኤዎች ለማስተናገድ ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ እንግዶችን ለማስተናገድ የሚያስችሉና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች መኖራቸው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙት ሆቴሎች ይሄን አገልግሎት በተሟላ ሁኔታ መስጠት የሚችሉ መሆናቸውን ዘርፉ ላይ የተሰማሩ አካላት ይናገራሉ፡፡ የአዲስ አበባ ሆቴሎች ማሕበር ሰብሳቢ አቶ ቢኒያም ብስራት፤ አሁን ያለውን የሆቴሎች አቅም የሚያብራሩት ቀደም ካሉት ዓመታት ጋር በማነፃፀር ነው፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት መሰል ስብሰባዎች ሲሰናዱ እንግዶች አዳራቸውን ወደ ቢሾፍቱና አዳማ ድረስ ለመሄድ ይገደዱ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ቢኒያም፤ አሁን በከተማዋ በቂ የሆቴሎች አቅርቦት መኖሩ የዘርፉን ውድድር አሳድጎታል፡፡ ይሄ ደግሞ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች አሉት፡፡ የሆቴሎች የአገልግሎት ተወዳዳሪነት ባደገ ቁጥር የዋጋ ተመጣጣኝነት ይጨምራል፡፡ ከዚያም እንግዶች ዓመት ጠብቀው ለስብሰባ ብቻ ከመምጣት ባሻገር የእረፍት ጊዜያቸውን ለማሳለፍ የሚመርጡበት ከተማ ወደመሆን ይቀየራል፡፡

‹‹የሆቴሎች ዋጋ ተመጣጣኝነት ከፍላጎትና አቅርቦት ጋር የተያያዘ ነው›› የሚሉት አቶ ቢኒያም፤ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ አገሮች ኤምባሲዎች ቅሬታ ሳያቀርቡ ይስተናገዳሉ፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ግን ከፍላጎቱ ጋር ያልተመጣጠነ አቅርቦት በመኖሩ ዋጋውም በዚያው ልክ ከፍተኛ እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ቢዝነስ ቱሪዝም›› የሚባለው ዘርፍ ሁሌም በውድድር የተሞላ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተለይም አዲስ አበባ ይሄን መልካም አጋጣሚ ለረጅም ጊዜ ስትጠቀምበት ቆይታለች፡፡ ነገር ግን አስፈላጊውን ነገር በየጊዜው ማሟላት ካልተቻለ ‹‹እርስት›› አይደለም፡፡ ስለዚህ ጠንክሮ መስራት የግድ ይላል፡፡

አቶ ቢኒያም ‹‹ያልተጠቀምንበት ትልቁ ሃብታችን›› ሲሉ የሚገልጹት የአገሪቱን ሰላምና ፀጥታ ብሎም የሕብረተሰቡ እንግዳ አክባሪነት ነው፡፡ ምክንያቱም ሰላም ‹‹በብር አይገዛም›› ይላሉ፡፡ የውጪ አገር እንግዳ ከሆቴሎች ወጥቶ በሰላም የማይመለስባቸው አገሮች መኖራቸውን በመጥቀስም፤ ኢትዮጵያ በአግባቡ ያልተመነዘረ ሃብቷን መጠቀም እንደሚገባት ይገልጻሉ፡፡ ሌላው አቶ ቢኒያም ‹‹በቀጣይ መሟላት አለባቸው›› የሚሏቸውን ጉዳዮች ሲጠቅሱ ካሉት መልካም ዕድሎች ጋር በማነፃፀር ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ዝናው ገዝፎ የናኘ አየር መንገድ ባለቤት ነች፡፡ እንዲሁም አዲስ አበባ አሁን ካሏት በተጨማሪ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት መቶ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ሊገነባት የምትችል ከተማ ነች፡፡ ስለዚህ ሁለቱ ቀዳሚ ጉዳዮች መልስ አግኝተዋል፡፡ ‹‹ታዲያ አዲስ አበባ የጎደላት ምንድን ነው?›› ከተባለ፤ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ሁሉንም ፍላጎቶች በአንድ ስፍራ ያካተተ ስብሰባ ማዕከል መሆኑን አቶ ቢኒያም ይገልጻሉ፡፡ የዚህ ማዕከል መኖር ከማስተናገድ ተልዕኮ ባሻገር መሰል ስብሰባዎችን አስተባብሮ የማምጣትም ሚና ይወጣል፡፡

እንዲህ አይነት አለም አቀፍ ስብሰባዎች ከተማዋን ይበልጥ በማስተዋወቅ በኩል ድርሻቸው የጎላ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ገብረጻድቅ ሐጎስ፤ ከተማዋ ይጎድላታል የተባለውን አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኤግዚቢሽንና ስብሰባ ማዕከል ለመገንባት የሚያስችሉ ስራዎች ተጀምረዋል፡፡ ለተግባራ ዊነቱም የከተማ አስተዳደሩ በስፔን ባርሴሎና ከሚገኝ አማካሪ ድርጅትና ከከተማዋ ንግድ ቢሮ በጋራ በመሆን ወደ ስራ ገብተዋል፡፡ በመስቀል አደባባይ በሚገኘው ኤግዚቢሽን ማዕከል በስምንት ነጥብ አምስት ኤክታር መሬት ላይ ይሰፍራል፡፡

ከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ ገፅታዋን በመልካም ጎኑ መቀየር መቻሏን የሚያነሱት አቶ ገብረፃድቅ፤ ከቀላል ባቡር ትራንስፖርት ባሻገር ከአንድ ሺ በላይ ዘመናዊ የቱሪስት ታክሲዎች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ከተማዋን ለእንግዶች ምቹ ያደርጋታል፡፡ ‹‹ጎብኚዎች በከተማችን የሚኖራቸው ቆይታ የተራዘመ እንዲሆን የተለያዩ ስራዎችን ጀምረናል›› የሚሉት ቢሮ ሃላፊው፤ የመጀመሪያው ተግባር በየዘርፉ ያሉ አገልግሎቶች ላይ ጥራትን ማሳደግ ሲሆን፤ የከተማዋን መዳረሻዎች ለማሳደግም እንጦጦን መልሶ የማልማት ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

በእንጦጦ በ4 200 ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባው የባሕል ማዕከል በአለም ባንክ ጥናት ተካሂዶ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ በአጠቃላይ በጥናት ደረጃ ለስብሰባ ማዕከሉ መቶ ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም የእንጦጦው ባሕል ማዕከሉ ወደ አራት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ታውቋል፡፡

የጎብኚዎችን ፍላጎት ለማርካት የሆቴሎችን ደረጃ እየተከታተሉ ማሳደግ ተገቢ ነው፡፡ ይሄን በማሰብም ለማሳደግና ለማስጠበቅም ቢሮው ባለፉት አራት ዓመታት ከ14 ሺ በላይ ሙያተኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲያገኙ ማድረጉን ይናገራሉ፡፡ ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ እስካሁን ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም አቶ ገብረፃድቅ ይገልጻሉ፡፡

እነዚህ ሁሉ ያልተቋረጡ ጥረቶች አዲስ አበባ ጎራ የሚሉ እንግዶች ከቤታቸው ያልራቁ ያህል ምቾት ተሰምቷቸው እንዲመለሱ የማድረግ ጥረት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ደግሞ ጎብኚዎች ከአካባቢያቸው ሲነሱ ጀምሮ በትኩረት የሚከታተሉት ነገር ሰላም ነው፡፡ ይሄን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ የምታሟላው አዲስ አበባ እንደ ወትሮው ሁሉ ሰሞኑንም የነዋሪዎቿን ግብረገብነት እያመሰገነች እንግዶቿን በሰላም ተቀብላ በፍቅር እየሸኘች ትገኛለች፡፡

 

ብሩክ በርሄ

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲሱ ተመራጭ ሙሳ ፋኪ ማሃማት ፤

 

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በሩዋንዳ ኪጋሊ ያልተሳካው የምርጫ ሂደት አዲስ አበባ ላይ መቋጫ አግኝቷል፡፡ በ28ኛው የሕብረቱ መደበኛ ስብሰባ ይበልጥ ተጠባቂ የነበረው የምርጫ ውጤት ከሁለት ቀን በፊት ሙሳ ፋኪ ማሃማትን የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡ ከአህጉሩ አመራርነት ፊታቸውን ወደ አገራቸው የፖለቲካ ተሳትፎ ለማዞር ‹‹በኮሚሽኑ የሚኖረኝ አመራርነት በዚህ ይብቃ›› ያሉት የ67 ዓመቷ ዶክተር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ፤ በርካታ ጅምር ሥራዎችን ለአዲሱ ተመራጭ በማሳለፍ ወደ አገራቸው ኤ ኤን ሲ ፓርቲ ተወዳዳሪነት አቅንተዋል፡፡ በመሆኑም አዲሱ ሊቀመንበር ከፊታቸው ‹‹የተለጠጡ›› አህጉራዊ ዕቅዶች ለማስፈፀም ቢሮ ተረክበዋል፡፡

የሕብረቱ ቀጣይ የቤት ስራዎች ምንድናቸው? የሚለውን ከማብራራታችን በፊት፤ ለመሆኑ አዲሱ ተመራጭ ሙሳ ፋኪ ማሃማት ማን ናቸው? ምን የኋላ ታሪክ አላቸው? የሚሉትን ጥቄዎች እንመልከት፡፡ የዛሬ 56 ዓመት እ..አ ሚያዝያ 21 ቀን 1960 በምስራቃዊ ቻድ ግዛት ቢልቲን ተወለዱ፡፡ በትምህርት ሕይወታቸው ከሪፐብ ሊክ ኦፍ ኮንጎ ‹‹ብራዛቪል ዩኒቨርሲቲ›› በሕግ የመጀመሪ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ የፖለቲካ ሕይወታቸውንም እ..አ ከ1980ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ወደ ‹‹ዴሞክ ራቲክ ሪቮሉሽነሪ ካወውስል›› በመቀላቀል ተጀምሯል፡፡

የወቅቱ የቻድ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ ስልጣን ሲይዙ እ..1991 ከስደት ዘመን በኋላ ወደ አገራቸው በመመለስ ብሔራዊ የስኳር ካምፓኒ ጨምሮ በተለያዩ የሚኒስትርነት ስልጣን ላይ አገልግለዋል፡፡ በመቀጠልም ከ1999 እስከ 2002 ድረስ በዴቤ አስተዳደር የካቢኔ ዳይሬክተር በመሆን ሰርተዋል፡፡ በ2001 ምርጫም የዴቤ የምርጫ ዘመቻ ዳሬክተር ሆነዋል፡፡ ከዚያም በሰራተኛና ትራንስፖርት ሚኒስትር እንዲሁም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እስከ መሆን ደርሰዋል፡፡ ከዚያም በ2005 የአገሪቱን የስልጣን ሚዛን ለመጠበቅ በሚል ከጠቅላይ ሚኒስትርነት መውረዳቸውን ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

በመጨረሻም በ2008 በጠቅላይ ሚኒስትር ዮሱፍ ሳላ አባስ አማካኝነት የአገሪቱ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ሲያገለግሉ ነበር፡፡ አምስተኛ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር በመሆን የተመረጡት ሞሳ ፋኪ፤ ከጋቦናዊው ጃን ፒንግ በመቀጠል ከመካከለኛው አፍሪካ የተመረጡ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ሲሆኑ እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይና አረብኛን አቀላጥፈው ይናገራሉ፡፡ በቀጣዮቹ አራት የስልጣን ዓመታት የሕብረቱን የተንዛዛ ቢሮክራሲ መስመር የማስያዝ ፍላጎት ያላቸው ፋኪ፤ በአህጉሩ ልማትን በማረጋገጥና ፀጥታውን አስተማማኝ በማድረግ የጥይት ሳይሆን የባሕላዊ ሙዚቃ ድምፅ የሚሰማባት አፍሪካ መፍጠር የሚል ሕልም እንዳላቸው ይነገራል፡፡

አዲሱ ሊቀመንበር በምርጫ ውድድሩ አራት ተፎካካሪዎች ቢያጅቧቸውም እስከመጨረሻው ሰዓት የተፎካከሯቸው የኬኒያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አሚና ሞሐመድ ነበሩ፡፡ በመጨረሻም የምርጫ ውጤቱ ይፋ ሲሆን አዲስ አበባ የሚገኘው መሰብሰቢ አዳራሽ በሁለት ተቃርኖ ስሜቶች ተሞልቶ እንደነበር የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ኤ ኤፍ ፒ ዘግቧል፡፡ ይኸውም በሕብረቱ ዋና ፅሕፈት ቤት የተሰበሰበው አብዛኛው የአገሮች ተወካይ ከፋኪ ይልቅ የዶክተር አሚናን መመረጥ በእርግጠኝነት ጠብቀው እንደነበር የሚያሳይ ነው፡፡ በተቃራኒው ቻዳውያን ግን በደስታ ተቃቅፈው ሲጨፍሩ እንደነበር ቦታው ላይ የተገኙ ብዙኃን መገናኛ ተቀባብ ለውታል፡፡

ድምፅ በመስጠት ለሰባት ዙሮች ከቀጠለው ብርቱ ፉክክር በኋላ አሸናፊነታቸው የተረጋገጠው ፋኪ ከፊታቸው ብዙ ዕቅድ አስቀምጠዋል፡፡ በተለይም የአህጉሪቱን ልማት ለማፋጠን በተለይ በናይጄሪያ፣ ማሊና ሌሎች ግዛቶች የሚንቀሳቀሱ የእስልምና አክራሪ ቡድኖችን ድርጊት መታገልን ቀዳሚ አጀንዳቸው ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡ ከምርጫው በፊት ባለው ሳምንት ‹‹ሬዲዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል›› ያነጋገራቸው አዲሱ ተመራጭ፤ ሕብረቱ ጠንካራ አመራር እንደሚያስፈልገው አበክረው ገልጸው ነበር፡፡ ለዚህም ሕብረቱ ከተለመደው አካሄድ ይልቅ አህጉሩ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት በሚችሉ ሂደቶች ላይ ማተኮር ይገባዋል፡፡

እስከ መጨረሻ የተወዳደሯቸው ኬንውያን ቢሆኑም ምርጫው ይፋ ከሆነ በኋላም ‹‹እንኳን ደስ አለዎት›› ለማለትም የቀደማቸው አልነበረም፡፡ ከመልካም ምኞት መግለጫው በተጓዳኝ ኬንያዊያን የሕብረቱ መሰረት በሆነው ‹‹ፓን አፍሪካኒዝም›› አጀንዳ ዙሪያ አብረው ለመስራት ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት አንፀባርቀዋል፡፡ በእርግጥ ይሄ አጀንዳ የኬንውያን ብቻ ፍላጎት አይመስልም፡፡ ነገር ግን በተለይ የሊቀመንበርነት ምርጫ ወቅት ተከትሎ በአህጉሩ ቀጠናዎች መካከል ልዩነት ፈጥሮ አቋሙ ሲንፀባረቅ መታየቱ ሕብረቱ መሰረቱን እንዳይዘነጋ ያሰጋል፡፡

ኬንያውያንም የሊቀመንበርነት ውድድሩ ወደ መካከለኛ ምስራቅ ሲያመራ የአህጉሩ ውህደትን ደጋግመው እንዲያነሱ ያስገደ ዳቸውም ለዚህ ይመስላል፡፡ በአዲሱ ሊቀመንበር የስልጣን ዘመን እርሳቸው ‹‹ፀጥታና ልማት›› ላይ ትኩረት እንደሚያ ደርጉ ቢገልጹም ሕብረቱ የጀመራቸው ብዙ የቤት ስራዎች አሉ፡፡ ከዚህ መካከል የተለያዩ አህጉራዊ የጋራ የልማት ዕቅዶችን ያካተተው አጀንዳ 2063፤ አንድ አፍሪካ አንድ ድምፅ፤ የሕብረቱን የፋይናንስ አቅም ማጎልበት፤ የአህጉሪቱን ወጣቶችና ሴቶች ድምፅ ማሰማት የሚሉት ከአንኳር ዕቅዶቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በመሆኑም በብዙዎች ዘንድ ሕብረቱ የሚገባውን ግርማ ሞገስ አለመላበሱን የሚጠቅሱ ትችቶች ለመከላከል በውስጥ ጉዳዮች ስራ ላይ ይበልጥ መበርታት ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቀዳሚነት ምርጫን ጠብቆ የሚስተዋለው ቋንቋ ላይ የተመሰረተ የቀጣና ልዩነት ፈጥኖ መገርሰስ አለበት፡፡ ይሄ መሆን ካልቻለ አፍሪካውያን በረጅም ጊዜ የያዙት የኢኮኖሚ ውህደት ጉዳይ ከዕቅድ የዘለለ ሊሆን አይችልም፡፡ አዲሱ ሊቀመንበርም ቅድሚያ ለሰጡባቸው አጀንዳዎ ቻቸው መሳካት ቅድሚያ በጋራ ስራዎች ላይ ቢያተኩሩ ችግርንም ቢሆን መከላከል የሚቻለው በሕብረት በመሆኑ ‹‹የጥይቱን ድምፅ ወደ ባሕል ዜማ›› የመቀየር ሕልማቸው እውን ሊሆን ይችላል፡፡

በሕብረቱ ኮሚሽን ታሪክ የአሁኑ ሊቀመንበር አምስተኛው ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ከምዕራብ አፍሪካ እንዲሁም አንድ ከመካከለኛው ምስራቅ በመጨረሻም አንድ ከደቡብ አፍሪካ ቀጣና የተወከሉ ሊቀመንበሮች ተፈራርቀው መርተው ታል፡፡ የመጀመሪያው እ..2002 እስከ 2003 ኮትዲቯራዊው አማራ ኢሴ በተጠባባቂነት፤ ከ2003 እስከ 2008 ማሊያዊው አልፋ ኦማር ኮናሬ፤ ከ2008 እስከ 2012 ጋቦናዊው ጃን ፒንግ እንዲሁም በመጨረሻ ከ2012 እስከ 2017 ደቡብ አፍሪካዊቷ ተሰናባች ዶክተር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ መምራታቸው ይታወሳል፡፡

 

ብሩክ በርሄ

 

Published in ዓለም አቀፍ
Thursday, 02 February 2017 17:30

መጓተትን ምን አመጣው?

 

ጨለማዋ አህጉር ስትባል የኖረችው አፍሪካ አሁን አሁን ብሩፍ ተስፋ ማየት ጀምራለች። ጥቅጥቁን የድህነት ጨለማ ለመግፈፍ ጥረት ከሚያደርጉት የአፍሪካ ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች። ከነበረችበት የብልጽግና ማማ ላይ ቁልቁል ስትንሸራተት የኖረችው አገር ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ግን በቃኝ በማለት ሽቅብ ጉዞ ጀምራለች።

ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ስለኢትዮጵያ በረሃብ ምክንያት ስለተፈጠረ እልቂት፣ በሽታ፣ የህጻናት ሞት፣ የትምህርት እጦት፣ የእርስ በርስ ጦርነት ከማውራት ይልቅ በርካታ ስኬቶች እያስመዘገበች ያለች አገር መሆንዋን መዘገባቸውን ቀጥለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በንጹህ መጠጥ ወሃ አቅርቦት፣ በእናቶችና ህጻናት ሞት ቅነሳ፣ በአገር ደረጃ በምግብ ራስን በመቻል፣ ድህነትን በመቀነስ እ ኤ አ ከ2000 እስከ 2015 .ም ተግባራዊ የተደረገውን የተባበሩት መንግስታት የሚሊኒየም የልማት ግቦች በማሳካት እውቅና አግኝታለች።

የኤሌትሪክ ሃይል በማመንጨት እና ቀጠናዊ የሃይል ትስስር ለመፍጠር በያዘችው እቅድና ባከናወነቻቸው ተግባራትም ትጠቀሳለች። በተተራመሰው የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የሰላም ደሴት ስለመሆኗ፣ የቀጠናውን ሰላም ለማስጠበቅ ስለምታደርገው ጥረት ይወራላታል። ድርቅ ችጋር አስከትሎ ዜጎቿን እንደቅጠል የሚያረግፍበትን የታሪክ ምዕራፍ በመዝጋታ ግንባር ቀደም ሆናለች፡፡

በኢትዮጵያ አሁን ከ95 በመቶ በላይ ህጻናቷ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት እድል አግኘተዋል። ግማሽ ያህሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አግኝተዋል። 1 350 በሚሆኑ በመለስተኛ ባለሞያነት በሚያሰለጥኑ የሞያና ቴክኒክ ተቋማት በሚሊዮን የሚቀጠሩ ወጣቶች የስልጠና እድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ከ33 በላይ በሚሆኑት ዩኒቨርሲቲዎቿ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከፍተኛ ባለሞያዎችን ማስተማር የምትችልበት ደረጃ ደርሳለች። ከ25 አመታት በፊት እነዚህ ስኬቶች ይደረስባቸዋል ተብለው የሚታሰቡ አልነበሩም።

ኢትዮጵያ ባለፉት 14 አመታት ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች። በ2007 በተከሰተው ከፍተኛ ድርቅ ምክንያት ይህ እድገት በ2008 .ም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደአንድ አሃዝ ወርዶ 8 በመቶ ሆኗል። ይህ የኢኮኖሚ እድገት ግን ብዙ አገሮች ተመኝተው አላሳኩትም። ከአምስት በመቶ አማካይ የአፍሪካ እድገት ጋር ሲነጻጸርም ከፍተኛ እድገት የሚባል ነው። በአጠቃላይ ከሰባት በመቶ በላይ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ነው።

መንግስት በአገሪቱ ለተመዘገቡ ያለፉት ዓመታት የኢኮኖሚ እድገት ለቀጣይ እድገትም የተመቻቸ ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል። ቀዳሚው አመቺ ሁኔታ ምቹ የኢንቨስተመንት ፖሊሲ ሲሆን ሌላው ለግዙፍ የመሰረተ ልማት ግንባታ ትኩረት መሰጠቱ ነው። ልዩ ተኩረት ከተሰጣቸውና ለኢኮኖሚው እድገት ወሳኝ ከሆኑት ግዙፍ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መካከል መንገድ፣ ሃይል፣ ቴሌኮም፣ ባቡር፣ የመስኖና የመጠጥ ወሃ አቅርቦት የመሳሰሉ ግንባታዎች ተጠቃሽ ናቸው። በእነዚሀ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ትልቅ ስኬት ተመዝግቧል። በአሁኑ ወቅትም በርካታ ግንባታዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

በመንገድ ልማት ዘርፍ፣ ከደርግ መውደቅ በኋላ ባሉት አምስት ዓመታት መንግስት በመንገድ መልሶ ግንባታ ፕሮግራም በጦርነት የተጎዱ መንገዶችን ከመጠገን ጎን ለጎን አዳዲስ የአስፋልት፣ የጠጠርና የገጠር የበጋ መንገዶች ግንባታን በማከናወን ነበር የመንገድ ዘርፍ መሰረተ ልማት የማስፋፋቱን ስራ የጀመረው። ከዚያ በኋላ በ1989 .ም የመንገድ ልማት ፕሮግራሞች ተቀርጸው ተግባራዊ ተደረገዋል። በዚህም ወደ 100 ሺ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ መንገድ ተገንብቷል። በ1983 .19 17 ኪሎ ሜትር ብቻ የነበረው የአገሪቱ መንገድ በ2003 .ም ወደ 110 414 ኪሎ ሜትር አድጓል። ልብ በሉ፣ ሃያ አመት በማይሞላ ጊዜ የአገሪቱ የመንገድ አቅም በስድስት እጥፍ ነው ያደገው።

የኤሌክትሪክ ሃይል መሰረተ ልማት ላይም ተመሳሳይ ድንቅ ስኬት ነው የተመዘገበው። አገሪቱ ከኤሌክትሪክ ሃይል ጋር ከተዋወቀችበት ከ1920ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ እስከ 1983 .ም ባሉት 60 ዓመታት እድሜ አጠቃላይ ይመነጭ የነበረው ሃይል 350 ሜጋ ዋት ብቻ ነበር። የኢትዮጵያ መንግስት ከደርግ ውድቀት በኋላ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብና የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል ወሳኝ የሆነውን የኤሌትሪክ ሃይል በከፍተኛ መጠን ለማምረት ወስኗል።

ይህን ተከትሎ አገሪቱ ያላትን እምቅ የኤሌክትሪክ የሃይል ምንጭ በመለየት ከፍተኛ ሃይል የማመንጨት ተግባር ተጀመረ። በዚህ መሰረት በርካታ የውሃና የንፋስ የሃይል ማመንጫዎች ተገንብተዋል። በአሁኑ ወቅትም አጠቃላይ የአገሪቱ ሃይል የማመንጨት አቅም 4 2 መቶ ሜጋ ዋት ገደማ ደርሷል። ይህ የሃይል መጠን በ1983 .ም ባሉት 60 አመታት በአጠቃላይ በአገሪቱ ይመነጭ የነበረውን ሃይል በ12 እጥፍ ያሳደገ ነው። 6 ሺ ሜጋ ዋት የሚያመነጨውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በርካታ የውሃና የንፋስ እንዲሁም የጂኦተርማል የሃይል ማመንጫዎች በመገነባት ላይ ይገኛሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ፤ ከህዝብ ቁጥር መጨመርና ገቢው እያደገ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ በብዙ እጥፍ የጨመረውን የስኳር ፍጆታ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በነበሩት የስኳር ፋብሪካዎች አቅም ማሟላት የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በተለይ ከ60 ዓመት በላይ ያገለገለውን የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሙሉ በሙሉ በአዲስ መተካት፤ የተቀሩትንም ነባር ፋብሪካዎች የማሻሻልና የማስፋፋት ስራ ከማከናወን በተጨማሪ አገሪቱ ለስኳር ምርት ያላትን እምቅ አቅም ተከትሎ አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎችን መገንባት አስፈላጊ ነበር።

በዚህ መሰረት በአፋር ተንዳሆ፣ በጣና በለስ፣ በኦሞ ኩራዝ እንዲሁም በወልቃይት የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ የ10 ግዙፍ ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ተጀምሯል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ከፋብሪካ ግንባታ ባሻገር የመስኖ መሰረተ ልማትም የሚሹ ናቸው። በመሆኑም ግዙፍ ብቻ ሳይሆን ከቴክኒክ አኳያም ውስብስብም ናቸው። የአብዛኞቹ ግንባታ ደግሞ በአገር በቀል ተቋራጮች ነበር የተጀመረው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዝናብ ላይ ጥገኛ ከሆነ ግብርና አርሶ አደሩን ለማላቀቅ በተለያዩ አካባቢዎች የመስኖና የንጽህ ውሃ አቅርቦት ግድቦች ግንባታ ተጀምሯል።

ከላይ ከብዙ በጥቂቱ የተነሱት ለአገሪቱ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትና ልማት ወሳኝ የሆኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መለስ ብለን ከ25 አመታት በፊት ከነበሩት ጋር ሲነጻጸሩ ድንቅና ታሪካዊ ስኬት ናቸው ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ፤ በብዙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ የአፈጻጸም ችግር ታይቷል። በተለይ የስኳር ፕሮጀክቶቹና የመስኖ ግድብ ግንባታዎች ላይ ከጊዜ አኳያ ከፍተኛ መጓተት ከወጪም አኳያ ግንባታቸው ሲጀመር ከተያዘላቸው ከእጥፍ በላይ እንዲፈጁ ያደረገ የአፈጻጸም ችግር ታይቷል። ይህ ሁኔታ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሯል። በመሆኑም ባለፉት ሁለት አመታት የተከናወኑትን የበርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ስኬት አደብዝዞት ከአፈጻጸም መጓተትና የወጪ ካለመጠን መጨመር ጋር የተያያዙ ችግሮች ብቻ ጎልተው እንዲታዩ አድርጓል። በግዙፍ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ዙሪያ በፍጹም ተገቢ ያልሆኑ የመጓተትና የወጪ መጨመር ችግሮች መኖራቸው ሳይዘነጋ ስኬታማ የነበሩትንም ማሰብ ተገቢ ነው።

ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበጀት አመቱ የስድስት ወር አፈጻጸም ዙሪያ ማብራሪያ ለመስጠት በተገኙበት ወቅት በግዙፍ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ዙሪያ ስላሉ ችግሮች ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎች ቀርበው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግዙፍ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ዙሪያ ሚዛናዊ የሆነ ማብራሪያ ነበር የሰጡት፤ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ በጉዳዩ ዙሪያ ያለውን እውነታ በግልጽ ስለሚያሳይ ልጠቅሰው ወድጃለሁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ማብራሪያ ሲሰጡ እንደተናገሩት፤ የግንባታ ዘርፍ ለአገሪቱ ገና አዲስ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የአመለካከትና የአቅም ችግር አጋጥሟል። በግንባታው ዘርፍ የሚስተዋለውን ችግር መፍታት ጊዜ ቢፈልግም የዘርፉ ዋነኛ ማነቆ የሆነውን የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ለማስቀረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

ከግዙፍ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም መጓተት አለ የሚለውን እየመረረ የመጣ ቅሬታ አስመልክተውም፤ «ሁሉም ፕሮጀክቶች አልተጓተቱም፤ ሁሉም ግን ጥሩ ሄደዋል ማለት አንችልም» ነበር ያሉት። በአገሪቱ ከተነገቡት ውስጥ ጥሩ አፈጻጸም አላቸው ብለው የባቡር ፕሮጀክቶችን ለአብነት ጠቅሰዋል። የኢትዮ- ጂቡቲ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ የቀላል ባቡር በተያዘላቸው ጊዜ ከተጠናቀቁት ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል። ከመንገድ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘም 82 በመቶዎቹ በተያዘላቸው ጊዜ እየተካሄዱ መሆኑንና 18 በመቶዎቹ ላይ ግን መጓተቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

የአውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታዎችም እንደ ስኬት ማሳያነት ተጠቅሰዋል። የሀዋሳ፣ ሽሬና ጂንካ አውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታ ከተያዘላቸው ጊዜ ቀደም ብሎ መጠናቀቁን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም፤ «ግንባታውን ያከናወኑትን የአገር ወስጥ ተቋራጮች ማመስገን ይገባል» ብለዋል። ከሀይል ማመንጫ ጋር ተያይዞም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከመስኖ ግድቦች እና ከከተሞች የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ላይ መጓተቶች መኖራቸውን አንስተውም «ለፕሮጀክቶቹ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ከአፈጻጸማችን ተረድተናል» ብለዋል። በዘርፉ የሚስተዋሉ የአቅምና የልምድ ማነሶችን ለመቅረፍም የውሃ ስራዎች ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት መቋቋሙን ገልጸዋል።

ከስኳር ፋብሪካዎች ጋር በተያያዘም የስኳር ፕሮጀክቶቻችን ከእቅድ ጀምሮ ችግር እንዳለባቸው መቀበል እንደሚገባም ተናግረዋል። አስሩን የስኳር ፕሮጀክቶች በአንድ ጊዜ መጀመራቸውን አስታውሰው «ይህ አቅምን የሚፈታተን ነበር» ብለዋል። ፕሮጀክቶቹ በተጀመሩባቸው አካባቢዎች ምንም አይነት የመሰረተ ልማት ያለመኖሩ አንዱ ችግር ነበር። ያበቃለት ዲዛይን ይዞ ወደስራ አለመግባትና ዲዛይኑን ከግንባታው ሂደት ጋር ለመስራት መወሰኑም ተጠቃሽ ነው። ያም ሆነ ይህ፤ «በስኳር ፕሮጀክቶቹ ያጋጠሙት ፈተናዎች ከባድ ቢሆኑም አሁን ላይ ግን ታልፈዋል» ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ግንባታውን በሚያከናውኑ ድርጅቶች በኩልም በተለይ የህንድ ኩባንያዎች የአቅም ማነስ ችግር እንደነበረባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካዎችን የሚገነቡት11 የህንድ ኩባንያዎች በፕሮጀክቱ መጀመር ማግስት በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት በአገራቸው ፍርድ ቤት ተካሰው በዚህ ሳቢያ ረጅም ግዜ ስራው መቋረጡ ይታወሳል። በቻይና ኩባንያዎች ግንባታቸው በመከናወን ላይ የሚገኙት ፕሮጀክቶች ግን የተሻለ አፈጻጸም ማሳየታቸውን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።

በአጠቃላይ አገሪቱ ባስመዘገበችው እድገትና በግዙፍ ፕሮጀክቶች አፈጻጻም ድንቅ ስኬቶች ቢመዘገቡም፣ በተለይ ከግዙፍ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ጋር በተያያዘ በወጉ ያልተሳኩትን ብቻ ሳይሆን የተሳኩትንም ማሰብ ተገቢ ነው። ኢትዮጵያ ለግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጀማሪ አገር መሆኗንም ማስታወስ ያሻል፡፡ ከፕሮጀክቶች አፈጻጸም ችግር ጋር በተገናኘ አሳሳቢውና ያለምህረት ልንታገለው የሚገባው ኪራይ ሰብሳቢነትን ነው።

ለፕሮጀክቶቹ መጓተት ምክንያት የሆኑ የአቅምና የካፒታል እጥረት ችግሮች አገሪቱ ከነበረችበት ሁኔታ የመነጨ በመሆኑ ከእድገታችን ጋር እየኮሰሰ የሚሄድ ነው። እናም ስለ ግዙፍ ፕሮጀክቶቻችን ስናስብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ሁሉም ፕሮጀክቶች አልተጓተቱም፤ ሁሉም ግን ጥሩ ሄደዋል ማለት አንችልም። እናም በጥሩ ከተከናወኑት የተገኘውን ልምድ፣ ችግር በገጠማቸው ላይ በመጠቀም በሂደት ወደ ተሻለ አፈጻጸም ማምጣትን እናስብ!

 

. ነጋሽ

Published in አጀንዳ

 

ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ ከምታስገባቸው ጥሬ እቃዎች መካከል ጎማና ተያያዥ ምርቶች ለማምረት የሚረዳው ግብአት ተጠቃሽ ናቸው። የዚህ ጥሬ እቃ ፍላጎትም እድገት እያሳየ ይገኛል። ወደ አገሪቱ የሚገቡት ተሽከርካሪዎች በከፍተኛ ደረጃ ከማሻቀባቸውም ጋር ተያይዞ የጎማ አቅርቦትን በውስጥ አቅም ለመሸፈን የሚደረገው ጥረትም በበቂ ደረጃ ምላሽ አላገኘም።

ጎማን ለማምረት የሚረዳው «ላቴክስ» የሚባለው ፈሳሽ ከጎማ ዛፍ ይገኛል። ዛፉ በኢትዮጵያ እንደሚገኝ ከተረጋገጠ ከመቶ አመት በላይ ሆኖታል። ይሁንና የተፈጥሮ ሀብቱን ጥቅም ላይ የማዋል ሃሳብ አስፈላጊ መሆኑ የታመነበት ቀድሞ «አዲስ ጎማ» በመባል የሚታወቀው ፋብሪካ የሚጠቀምበትን ግብአት ከውጭ ጥገኝነት ለማላቀቅ ነበር።

የጎማ ዛፍን በአገር ውስጥ በማልማት ከውጭ ጥገኝነት ለመላቀቅ ከአስራ ዘጠኝ ሰማንያዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ፕሮጀክት ተነድፎ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል። በተደረገውም የዳሰሳ ጥናት በአገሪቱ ለጎማ ዛፍ ልማት ምቹ የሆነ 84 ሺ ሄክታር መኖሩ ተረጋግጧል። ይሁንና በአሁኑ ወቅት በኬሚካል ኢንደስትሪ ኮርፕሬሽን ስር በሚገኘው የጎማ ዛፍ ልማትና ምርት ፕሮጀክት ስር ማልማት የተቻለው 2 700 ሄክታር ብቻ ነው። ከዘርፉ በቂና ጥራት ያለው ግብአት በአገር ውስጥ በማምረት ከጥገኝነት መላለቅ አልተቻለም። ለአብነት ሆራይዘን አዲስ ጎማ አምና 220 ሚሊዮን ብር በማውጣት ለምርቱ ግብአት የሚሆን ጥሬ እቃ አስገብቷል።

ኢትዮጵያ የጎማ ዛፍ ለማልማት ምቹ የአየር ጸባይ አላት። ከአለው እምቅ አቅም አንጻር ጥቅም ላይ የዋለው እጅግ አናሳ መሆኑ ግን ብዙ ክፍተት እንዳለ ጠቋሚ ነው። ጥሬ እቃውን ለመግዛት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ከማስቀረት ባሻገር በአገር ውስጥ የሚፈጥረውን የስራ እድል መጠቀም አለመቻሉ ጉድለቶችን ፈትሾ የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚገባ ያሳያል።

ምንም እንኳን መንግስት የጎማ ዛፍ ልማት አስፈላጊ መሆኑን በማመን መርሃግብር አዘጋጅቶ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ቢሆንም የሚጠበቀው ለውጥ ላለመምጣቱ ለዘርፉ በቂ በጀት አለመመደቡ እንደ አንድ ችግር ይነሳል። በእዚህም ከሁለት አስርት አመታት በላይ የዘለቀው ፕሮጀክት በብዛትም ይሁን በጥራት በቂ ግብአት ማቅረብ አልቻለም። መንግስት ያለውን እምቅ አቅም የሚመጥን በጀት በመመደብ ከውጭ ጥገኝነት መላቀቅ የሚቻልበትን መንገድ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል።

የጎማ ዛፍ ከተተከለ በኋላ ለምርት እስከሚደርስ ስድስት አመት እንደሚወስድ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህም በየወቅቱ ደርሰው ምርት ከሚታፈስባቸው ሰብሎች አንጻር ሲመዘን አርሶአደሮች ወደ ዘርፉ እንዳያተኩሩ አድርጓቸዋል። የሌሎች አገሮች ተሞክሮ እንደሚያመለክተው በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ አርሶአደሮች የማበረታቻ ፖሊሲ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህ በአገራችን አለመተግበሩ አርሶአደሮች በብዛት እንዳይሰማሩ እክል ስለሚፈጥር የሚመለከተው አካል ክፍተቱን የሚደፍን የፖሊሲ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ወሳኝ መሆኑን በማመን መስራት ይገባል። ዘርፉ የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመን በመሆኑ የማበረታቻ ማእቀፎችም ሊበጁለት ግድ ይላል።

በዘርፉ በምርምር ረገድ የተሰሩት ስራዎች ውስንነትም ሌላው ጉድለት ነው። ባላቸው ምቹ ያልሆነ የአየር ንብረትና ውስን መሬት የጎማ ዛፍን የኢኮኖሚ ዋልታቸው ያደረጉ አገራት ተሞክሮ እንደሚያመለክተው በምርምሮች ምርታማነትና ጥራትን ማሻሻል ይቻላል። ዘርፉን በሚመለከት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ስልጠናዎች ይሰጣሉ። በሀገራችን ግን በኢትዮጵያ የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል ከሁለት አመት ወዲህ ከሚያደርገው ጥረት የተለየ በምርምር የታገዘ ስራ አልተሰራም። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከዘርፉ የሚገኘውን ትሩፋት ግምት ውስጥ በማስገባት የምርምር የትኩረት አቅጣጫቸው ማድረግ አለባቸው።

በአሁኑ ወቅት በመልማት ላይ የሚገኘው የጎማ ዛፍ ጥራት ያለው ግብአት ከማስገኘት አንጻር ውስንነቶች እንዳሉበት መረጃዎች ያመለክታሉ። የተሻለ ዘር መርጦ ከማስፋት ጀምሮ ምርቱን በመሰብሰብና ለጎማ ማምረቻ ግብአት እስከሚሆን ድረስ ያለው ሂደት ዘመናዊ አሰራርን ተከትሎ እንዲከናወን በዘርፉ የበለጸጉትን አገራት ተሞክሮ መጋራት አስፈላጊ ነው። ጉድለቶቹ በሙሉ ታርመው ያለውን እምቅ አቅም መጠቀም ከተቻለ ከውጭ ጥገኝነት ከመላቀቅ ባሻገር ለብዙ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ይቻላል።

 

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።