Items filtered by date: Friday, 03 February 2017

 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር 15ተኛ ሳምንቱን ይዟል። እስከ አሁን ድረስ ጨዋታዎቹ በተያዘላቸው መርሀ ግብር እና ስፍራ መሰረት እየተካሄዱ ነው። ሆኖም ግን በአንዳንድ ጥቃቅን ምክንያቶች የሰአት እና የቦታ ለውጥ መኖሩ አልቀረም። ነገና ከነገ በስቲያ የሚደረጉት ጨዋታዎችም በተያዘላቸው የመርሀ ግብር መሰረት ይካሄዳሉ።

የዝግጅት ክፍላችን ዛሬም እንደተለመደው ነገ እና ከነገ በስቲያ የሚደረጉ ጨዋታዎችን እና አንዳንድ መረጃዎችን ይዞላችሁ ቀርቧል። ውድድሩን ቅዱስ ጊዮርጊስ እየመራው ሲሆን አዳማ ከተማና ደደቢት እየተፈራረቁ የሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን እየያዙ ይገኛሉ። በአንፃሩ የዚህን አመት ውድድር ከወዲሁ «ይሄ ክለብ ይበላዋል» የሚል ግምት ለመስጠት አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም መሪውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታዮቹ በቅርብ እርቀት እየተከተሉት ይገኛሉ።

15ተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አብዛኞቹ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ከተማ ይደረጋሉ። በዚህ አጋጣሚ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አንድ ጨዋታን ያስተናግዳል።

ቅዳሜ ጥር 27

9 ነጥብ የደረጃውን ግርጌ የያዘው አዲስ አበባ ከተማ፤ በእለተ ቅዳሜ ከወልድያ ጋር በ9 ሰአት በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚገናኝ ይሆናል። ክለቡ ባሳለፍነው ሳምንት መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግዶ አንድ አቻ መውጣቱ የሚታወስ ነው። ወልዲያም በተመሳሳይ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ጋር ባሳለፍነው ሳምንት ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱ ይታወሳል።

በዚያው እለት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ11 ሰአት 30 በአዲስ አበባ ስታዲየም ይገናኛል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘንድሮው አመት ሊጉን ከተቀላቀለው አዲስ አበባ ከተማ ጋር ባሳለፍነው ሳምንት ተገናኝቶ ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱ የሚታወስ ነው። በዚህም ነጥቡን ከተከታዮቹ የማስፋቱን እድል አምክኖታል። በአንፃሩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባሳለፍነው ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረገው ጨዋታ የ 52 ሰፊ ሽንፈት ደርሶበታል።

እሁድ ጥር 28

አብዛኞቹ ጨዋታዎች በእለተ እሁድ ይከናወናሉ። የእረፍት ቀናቸውን እግር ኳስ በመመልከት ማሳለፍ ለሚፈልጉ ሰዎች ይህ ጥሩ አጋጣሚ ነው። በዚህም ጅማ አባ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ በ9 ሰአት በጅማ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው። ጅማ አባ ቡና ባሳለፍነው ሳምንት በሀዋሳ የ21 ሽንፈት እንዳጋጠመው ይታወሳል።

በሌላ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና በ9 ሰአት በአርባ ምንጭ ስታዲየም፤ መከላከያ ከሲዳማ ቡና በ9 ሰአት በአዲስ አበባ ስታዲየም፤ ፋሲል ከተማ ከአዳማ ከተማ በ9 ሰአት በጎንደር ስታዲየም፤ ደደቢት ከወላይታ ድቻ በ9 ሰአት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሀዋሳ ከተማ በ11 ሰአት ከ30 በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።

የዝግጅት ክፍላችን የእረፍት ቀናችሁን በተሳካ ሁኔታ እንድታሳልፉ ይፈልጋል፤ የምትደግፉት ቡድን አስደሳች ውጤት እንዲያስመዘግብላችሁም ከወዲሁ ይመኛል። ሰላም!

 

ዳግም ከበደ

 

 

Published in ስፖርት

በአለም እግር ኳስ መድረክ ላይ ተወዳጅነት ካተረፉ ጥቂት ክለቦች መካከል ባርሴሎና ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል ብንል ማጋነን አይሆንም። ክለቡ በአሁኑ ሰአት የተመዘገቡ 162 ሺ አባላቶች ሲኖሩት « ካምፕ ኑ» የሚል ስያሜ ያለው በአውሮፓ ትልቁ ስታዲዮም ባለቤት ነው። በተለይ ከክለቡ ጋር ወዳጅነታቸው የጠበቁ በርካታ አባላቶችን በማሰባሰብ አሁንም በአውሮፓ ውስጥ የመጀመሪያውን ስፍራ ይይዛል።

በስፔን ስር ለሚተዳደሩት « የካታላን» ህዝቦች ባርሴሎና ከአንድ እግር ኳስ ክለብ በላይ ትርጉም አለው። የባርሴሎና ክለብ ለህዝቡ ብሄራዊ ኩራታቸው እና መገለጫቸው አድርገው ይቆጥሩታል። ከዚህ ቀደም እነዚህ የካታላን ማህበረሰቦች ይደርስባቸው የነበረውን የፖለቲካ ጫና እና ጭቆና፤ በተለይም « በጀነራል ፍራንሲስ ፍራንኮ» የአገዛዝ ዘመን ተቋቁመው ያለፉትን በደል ማስታወሻ ብሎም መዘከሪያ አድርገው ነው የሚወስዱት።

ካታላንያን ባርሴሎናን ከ« እግር ኳስ ክለብ» በላይ አድርገው የማንነታቸው መገለጫ እንዴት እንዳደረጉት፣ አመሰራረቱ፣ የድል ዘመኖቹ እና አስቸጋሪ ጊዜያቶቹን አልፎ በምን መልኩ አሁን ያለበት የዝና ማማ ላይ በክብር እንደተቀመጠ በዛሬው ዘገባችን ለመዳሰስ እንሞክራለን። በአገር ውስጥ ዘገባዎቻችን « የክለቦች መፍረስ ፈተና እና ወድቀት» ላይ ከዚህ ቀደም በርካታ ዳሰሳዎች ማድረጋችን ይታወቃል፤ የዚህን ክለብ ውጣ ውረድ እና ታሪክ መዳሰሱ፤ ለአገራችን ክለቦች ችግር መፍትሄ ይጠቁማል የሚል እምነትም አሳድሮብናል። መልካም ንባብ።

የካታሎናውያን ባለውለታ

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ1819 ባርሴሎና የእግር ኳስ ክለብ ተመሰረተ። የዛሬው ታላቅ ክለብ ምስረታን የጠነሰሰው ሲውዘርላንዳዊው ሀንስ ማክስ ጋምበር ነው። ብስክሌት መጋለብ፣ጎልፍ፣እግር ኳስ እና ራግቢን መጫወት ከልቡ የሚወደው ብላቴና ከእናቱ ሞት በኋላ ወደ ዙሪክ በመሄድ ኑሮውን እዚያው መሰረተ። ከጥቂት አመታት ቆይታ በኋላ ግን በአፍሪካ የሚገኝ የስኳር ካምፓኒ ላይ ለመስራት ወደዚያው አቀና ። እዚያ ለአንድ አመት እንደቆየም አያቱን ለመጠየቅ በሚል ሰበብ ወደ ስፔን ባርሴሎና ከተማ ተጓዘ። ባርሴሎና እንደደረሰ ግን በከተማዋ ውበት ተማርኮ እዚያው ለመቅረት ወሰነ። ስፓኒሽ እና የካታላን ቋንቋን ተምሮ ስሙን በአገሬው ባህል ቀየረ «ዮሀን ጋምበር» በሚል።

ይህ ብላቴና ስፖርት በተለይ የእግር ኳስ ወዳጅ በመሆኑ፤ በስፔን ባርሴሎና «ላስ ዲፖርቴ» በሚባል መፅሄት ላይ የስፖርት ኤዲተር ሆኖ መስራት ጀመረ። ለስራው መሰረት የሆነው ደግሞ በሲውዘርላንድ ብራስልስ ከተማ ላይ በሚገኝ የባዜል እግር ኳስ ክለብ የቡድን አንበል ሆኖ መጫወቱ ነበር። ጥቂት በስራው ላይ እንደቆየ ግን አንድ ሀሳብ ይመጣለታል። ከተማዋን እና እርሱ የሚኖርበትን ማህበረሰብ የሚወክል አንድ ክለብ ሟቋቋም።

1899 ዮሀን ጋምበር በሚሰራበት መፅሄት ላይ ክለብ የማቋቋም ህልም እንዳለው ገልፆ ይህንን ሀሳቡን ማህበረሰቡ እንዲደግፍለት ጥሪ አስተላለፈ።ሀሳቡ በጓደኞቹ እና በበርካታ የስፖርት ወዳጅ ቤተሰቦች ተቀባይነት አገኘ። በህዳር 29 እርሱ እና ሌሎች አስር ጓደኞቹ «ባርሴሎና የእግር ኳስ ክለብ»ን ወደ ስፖርት አለሙ አቀላቀሉት። በምስረታው ላይ የሀሳቡ ጠንሳሽ ዮሀን ጋምበር የክለቡ አንበል በመሆን መጫወት ጀመረ። የመጀመሪያ ጨዋታቸውንም ከእንግሊዝ ስደተኞች ጋር በማድረግ 10 በሆነ ውጤት ተሸነፉ። የክለቡ ፕሬዚዳንት በመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ እንግሊዛዊው ጉዋልተሪ ዋይልድ ተመረጠ።

1908 ጋምበር የክለቡ ፕሬዚዳንት ሆኖ ማገልገል ጀመረ። እስከ 1925 ድረስም ለአምስት ጊዜ ተመርጦ ቆየ። የመጀመሪያ ስኬቱንም 6 ሺ ተመልካቾች የመያዝ አቅም ያለውን «ላ እስኮፒዶራ» ስታዲዮምን በማስገንባት ጀመረ። በከተማዋ በተለይም በካታላንያን ዘንድ ክለቡ ተወዳጅነትን እያተረፈ መጣ። በርካታ ጨዋታዎችን እና የሊግ ተሳትፎዎችን ማድረግ ጀመረ።

ሰኔ 1925 ለባርሴሎና ክለብ መስራች ዮሀን ጋምበር አስደሳች ጊዜ አልነበረም። በወቅቱ የስፔን ብሄራዊ ቡድን ከእንግሊዝ አቻው ጋር ጨዋታ ያደርግ ነበር። በዚህ ወቅት ካታላናዊያን የስፔን ብሄራዊ መዝሙርን በመተው የእንግሊዝን መዘመር ይጀምራሉ። በዚህ የተበሳጨው የንጉሳውያን ዘር ያለው እና የሪያል ማድሪድ ደጋፊ ፕሪማ ዲ ሪቪዬራ በጋምበር ላይ ክስ በመመስረት ከአገር እንዲወጣ አደረገው። የባርሴሎና ስታዲየምንም ለ6 ወራት እንዲዘጋ አዘዘ። ዋንኛው ምክንያትም ካታላንያን የራሳቸውን ማንነት እንዲያቀነቅኑ መንገዱን አመቻችቷል በሚል ነበር። ከዚያን ወቅት ጀምሮ ነገሩ ከመቀዝቀዝ ይልቅ የባርሴሎና ክለብ የካታላን የነፃነት እና የብሄራዊ ማንነት ማቀንቀኛ ተደርጎ ይወሰድ ጀመር። አሁንም ድረስ በስፔን ውስጥ ይህ አይነት ስሜት ይንፀባረቃል። ከስፔን እንዲባረር የተደረገው ጋምበር ግን በድብርት እና በጭንቀት ምክንያት በአገሩ ሲውዘርላንድ በ52 አመቱ እራሱን አጥፍቶ ሊሞት ችሏል። ለዚህ ታላቅ ሰው ግን ካታላንያን ቦታ አላጡለትም። በባርሴሎና አንድ መንገድ በስሙ ሰይመውለታል።

ወርቃማው የባርሴሎና ዘመን

1919 እስከ1929 ድረስ የባርሴሎና ወርቃማው ዘመን እንደነበር ይታመናል።በ1922 ባርሴሎና 30 ሺ ተመልካች የመያዘ አቅም ያለው «ኤል ካምፕስ ዴልስ ኮርትስ» የሚል ስያሜ የተሰጠው ስታዲየም ማስገንባት ቻለ። በዚሁ አስር አመት ውስጥ ደግሞ ጣፋጭ የእግር ኳስ ድሎችን ማጣጣም ጀመረ። የመጀመሪያውን የላሊጋ ዋንጫ አሳካ። ይህም ብቻ አይደለም ለ8ተከታታይ አመታት የካታላን ሊግ አሸናፊ እና ለ5 ጊዜያት «የስፓኒሽ ካፕ» ድል ባለቤት ሆነ። በዚሁ ጊዜ ስታዲየሙ ተመልካቾች የመያዝ አቅሙን ወደ 60ሺ አደረሰ የክብር ስሙንም « ካቴድራል ኦፍ ፉትቦል» በሚል ሰየመ።

1930 በኋላ ግን ለክለቡ አስጨናቂ እና የመከራ ዘመን ነበር። ክለቡ በገንዘብ ቀውስ ውስጥ በዚህ አመት የገባ ሲሆን ከዚህም ሌላ በርካታ የመከራ አመታትን አሳልፏል። ከዚህም ውስጥ የስፔን የርስ በርስ ጦርነት የማይለቅ አሻራውን በክለቡ ላይ አሳርፏል። ወትሮውንም በባለስልጣናት እና በስፔን ገዝዎች ተወዳጅ ያልሆነው ክለብ፤ በርስ በርስ ጦርነቱ በጀነራል ፍራንኮ ፍራንሲስ ስር በሚተዳደር ወታደር ፕሬዚዳንቱ ጆሴፍ ሲንዮል በ1936 ተገደሉ። በዚያን ወቅት የክለቡ ተጫዋቾች በአሜሪካ እና በሜክሲኮ የጨዋታ ጉዞ ላይ የነበሩ ሲሆን፤ ግማሽ ያህሉ ግድያውን እና የፖለቲካ ቀውሱን ተከትሎ ሳይመለሱ ቀሩ።

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በ1938 በስታዲየሙ ላይ የቦምብ ጥቃት ደረሰበት። በዚህም መቀመጫዎቹ እና በርካታ ቁሶች ወደሙ። በዛኑ ወቅት የክለቡ አመራር በጀነራል ፍራንኮ አፍቃሪ ባለስልጣን ተቀየረ። በዚህ አጋጣሚም የካታላንን ማንነት የሚያቀነቅነው የክለቡ ስያሜ «ክለብ ደ ፉትቦል ባርሴሎና» በሚል እንዲቀየር ተደረገ። በዚህ ጊዜ 25 ሺ ደርሶ የነበረው የደጋፊ አባል ወደ 3500 አሽቆለቆለ። የክለቡን ክብር በሚገልፅ ሁኔታ በአራት ቀይ መስመር የተመሰረተ ማሊያው በሁለት ቀይ መስመር እንዲለወጥ ተደረገ። (እስከ 1973 ድረስም ይህ ማሊያው ሳይቀየር ቆይቷል)

የተመለሰው ጣፋጭ ድል

በፖለቲካ እና በተለያዩ ውስጣዊ ጫናዎች ስር ወድቆ የነበረው ባርሴሎና በ1940 ዳግም ማንሰራራት ጀመረ። በ9አመታት ውስጥም ራሱን አጠናክሮ የበርካታ ዋንጫዎች ባለቤት ሆነ። 21 የካታሎን ሻምፒዮን ሺፕ ድሎችን በማጣጣም፣9ዋንጫዎችን እና አራት ጊዜ የስፓኒሽ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን አሸናፊ መሆን ቻለ። የደጋፊ አባላቶቹም ቀድሞ ወደነበረበት እየተመለሰ መጣ። በተለይ በ1951/52 የውድድር ዘመን ወርቃማ ጊዜያትን ክለቡ ማሳለፍ ችሏል። በዚህ አመት የላሊጋ፣ላ ኮፓ ዴላሬ፣ ዘላቲን ካፕ፣ዘኢቫ ዱዋርት ካፕ፣ ዘማርቲኒ ሮዚ ትሮፊን በአጠቃላይ በአንድ አመት 5 ዋንጫዎችን የግሉ አደረገ። በዚህም የቡድኑ ስብስብ «ባለ አምስት ዋንጫው» የሚል ስያሜን አግኝቷል። ደጋፊ አባላቶቹም 30 ሺ ሊደርሱ ችለዋል።

ክለቡ ተወዳጅነቱ በጨመረ ቁጥር የአባላቱም ቁጥር ይበልጥ አሻቀበ። በዚህ የተነሳ አዲስ የስታዲየም ግንባታ አስፈለገ። እስካሁን ድረስ የሚጠቀሙበትን እና ተወዳጁን «ካምፕ ኑ» ስታዲየም ገነቡ። ይህ ግዙፍ ስታዲየም 90ሺ ተመልካች እንዲይዝ ተደርጎ በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ተደረገ። ስታዲየሙ በተገነባ ሶስት ተከታታይ አመታት ክለቡ ውጤት ርቆት ቆየ። ይህ ግን አባላቱን እና ደጋፊዎቹን ከመጨመር አላገደውም ነበር። ምክንያቱም ባርሴሎና ለካታላን ህዝብ ከእግር ኳስም በላይ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ትርጉም ነበረው።

የካታሎንን ልብ ያሸነፈው ዮሀን ክሩፍ

1973 የባርሴሎና አመራሮች አንድ ውሳኔ አሳለፉ። ይህ ውሳኔያቸው በርካታ ክርክሮችን እና ውይይቶችን አልፎ የተወሰደ ነበር። አወዛጋቢው ጉዳይ የተከሰተው የእግር ኳስ ጠበብቱን ዮሀን ክሩፍ በመቅጠር እና ባለመቅጠር ላይ ነበር። ነገሩ ግን ክሩፍን በመቅጠር ተቋጨ። ጉዳዩ አከራካሪ የነበረው የውጪ ዜግነት ባላቸው ተጫዋቾች ላይ የክለቡ ህግ ጠበቅ ያለ ስለነበር ነው። ሆኖም ግን ክሩፍ የደጋፊዎችን እና የክለቡን አመራሮች ቀልብ ብዙም ሳይቆይ መሳብ ቻለ። በ1973 ባርሴሎናን የተቀላቀለው ብላቴና በርካታ ድሎችን እና ጣፋጭ ጊዜያትን ለማግኘት ቁልፉ ሰው ሆነ። በተለይ ይህ ተጫዋች በ1974 ክለቡ የስፓኒሽ ሻምፒዮንሺፕ ባለድል ሲሆን የአንበሳውን ድርሻ ይወስድ ነበር። ድሉን ሲያስመዘግቡ ደግሞ የምንጊዜም ተቀናቃኛቸውን የሪያል ማድሪድ ክለብ 50 መርታት ችለው ነበር።

አመታት ወደፊት ይነጉዷሉ። እግርኳስም አለም አቀፍ ተወዳጅነቱ ይበልጥ እየናረ መጥቷል። በስፔን የማይገረሰስ የሚመስለው እና በአምባገነን አገዛዙ የሚታወቀው ፍራንኮ ህይወት አለፈ። በአገሪቷ ዴሞክራሲ ታወጀ። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ለባርሴሎና የእግር ኳስ ብሎም ለካታሎናውያን የደስታ ዘመን ፈጠረ። የክለቡ አባላት በነፃ ምርጫ ጆሴፍ ሊውስ ኑንዝን አዲስ ፕሬዚዳንታቸው አድርገው መረጡ (እኚህ ሰው እስከ 2000 ድረስ በፕሬዚዳንትነት ለረጅም ዘመን በማገልገል አቻ አልተገኘላቸውም)። በ1980 ግን ባርሴሎናን የእግር ኳስ ውጤት ራቀው ደጋፊዎች እና የክለቡ ወዳጆች እጃቸውን ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ላይ ቀሰሩ። ቦርዱ ከስልጣን እንዲለቅ ተቃውሟቸውን አሰሙ። ጉዳዩ እየተጓተተ 1988 ድረስ ተጓዘ። በዚህ ጊዜ ግን አንድ አስደናቂ ነገር ተከሰተ። ዮሀን ክሩፍ የተጫዋችነት ዘመኑ ተጠናቆ በድጋሚ ወደ ባርሴሎና ቤት በአሰልጣኝነት ተመለሰ። በጨዋታ ዘመኑ የባርሴሎና ደጋፊዎችን እና ቤተሰቦችን ቀልብ ስቦ ነበር።

አሰልጣኝ ዮሀን ክሩፍ በውጤት ማጣት ይሰቃይ የነበረውን ባርሴሎና በአዲስ ፍልስፍና ወደ ድል ዙፋኑ በድጋሚ መለሰው። «ቲኪ ታካ» ወይም ቶታል ፉትቦል የሚል ፍልስፍናን ይዞ የመጣው ክሩፍ፤ ለአራት ተከታታይ አመታት ባርሴሎና የላሊጋው ባለድል እንዲሆን አስቻለው። ከዚህም ሌላ በክለቡ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን «የኢሮፒያን ካፕ» ሻምፒዮና ድል ባለቤት አደረገው።

በዚህ ክለብ ውስጥ በርካታ የአለማችን ኮከቦች ተጫውተው ያለፉ ሲሆን አሁንም ድረስ በክለቡ እየተጫወተ የሚገኘው ምትሀተኛው አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲን አንዱ ነው። ሮናልዲንሆ ጎቾ፣አፍሪካዊው ኮኮብ ሳሙኤል ኢቶ፣ጋርዲዮላ፣ኢኒዬስታ፣ዣቪ፣ዳንኤል አልቬስ እናም ሌሎች ተደናቂ ኮከቦች በካታላን ማንነት ላይ አሻራቸውን አሳርፈዋል።

ባርሴሎና ከላይ ካወሳናቸው የመውደቅ እና የመነሳት ታሪክ ውስጥ በተለየ መልኩ የማይዘነጋው እና በታሪክ መዝገቡ ሚዛን የሚደፋ ክስተትም አስተናግዷል። ይህ ሁነት ከ2008 እስከ 20012 የተስተናገደ እና የአለምን ቀልብ በእጅጉ የሳበ ነበር። በዮሀን ክሩፍ የአሰልጣኝነት ዘመን በተጫዋችነት ያሳለፈው ጆሴፕ ጋርዲዮላ የባርሴሎናን ቤት በዋንጫ ያጥለቀለቀበት የፍሰሀ ዘመን። በዚህ አመት 14 ዋንጫዎችን ክለቡ ማሳካት ችሏል። በአራት አመት ጊዜ ውስጥ የስፓኒሽ ሻምፒዮንሺፕን በ2009/10/11 ለሶስት ተከተታይ አመታት ሲያነሳ፤ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን በ2009 እና 2011 ማሳካት ችሏል። በተመሳሳይ በ2009/10/11 የስፔን የንጉሱ ዋንጫን ጠራርጎ ወስዷል።

ባርሴሎና ከአንድ የእግር ኳስ ክለብ በላይ የመጨቆን ድምጽ ተምሳሌት ነው። የኮከቦች መፍለቂያ፤ የካታሎን ማንነት መገለጫ። የፖለቲካ ጫና እና ጭቆና መገርሰሻ፤ የብሶት መግለጫም ተደርጎ ይቆጠራል። ለዚህም ነው የስፔን ካታሎናውያን በድል ያምበሸበሻቸውን ክለብ በድጋፍ ድምፃቸው «"Més que un club"More than a club» ከክለብም በላይ የማንነታችን መገለጫ በማለት ሲጠሩት የሚደመጠው።

 

ዳግም ከበደ

 

 

Published in ስፖርት
Friday, 03 February 2017 18:17

በ93 አመታቸው 107 ሚስቶች

 

ልጅ ፀጋ ነው፤ ልጅ በዕድሉ ያድጋል ወይም ልጅ በረከትን ይዞ ይመጣል…ወዘተ የሚሉ አባባሎች በሀገራችን ልጅ መውለድን የሚያበረታቱ ሥነ ቃሎች ናቸው፡፡ የናጄሪያው አዛውንት ግን ከአባባሉም በላይ ልጅ በልጅ ሆነዋል፡፡ አዛውንቱ ይህችን ዓለም እስኪሰናበቱ ድረስ ዕድሜ ሳይገድባቸው ሚስት ሲያገቡና ልጅ ሲወልዱ ነው የኖሩት፡፡ እስከ93 ዓመት ዕድሜያቸው ድረስ ያፈሯቸው ልጆችና ያገቧቸው ሴቶች ብዛት አግራሞትን ፈጥሯል፡፡ አዛውንቱ በ57 ሚስቶቻቸው የብረት መዝጊያም ተብለው ተመስክሮላቸዋል፡፡ ከቀናት በፊት ይህችን ምድር ስለተሰናበቱት የብዙሃን አባት ልንገራችሁ፡፡

በሙሉ ስማቸው አል ሃጂ መሃመድ አቡበከር ቤሎ ማሳባ ተብለው የሚጠሩት አዛውንት በናይጄሪያ ኒጀር ግዛት በምትገኘው ቢዳ የተባለች አካባቢ ዘራቸውን እንደ ሰማይ ከዋክብት ሲያበዙ የኖሩ ሰው ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ማሳባ በህይወት ዘመናቸው 107 ሴቶች አግብተዋል፡፡ ከመካከላቸው ግን አስሩን ፈተዋቸዋል፡፡ይህችን ምድር እስከተሰናበቱበት ዕለት ድረስም ከቀሪዎቹ ከ97ቱ ጋር ነው በትዳር የኖሩት፡፡ ከ187 በላይ ልጆች እንደነበሯቸውም ተጠቅሷል፡፡ ገና ነፍሰጡር የሆኑት ሚስቶቻቸው ሲወልዱ ደግሞ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ከፍ ይላል፡፡

የሸሪአን ህግ የተላለፉት ማሳባ በቢዳ ኤሚሬትስ ምክር ቤትና በእስላማዊ መሪዎች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ በተደጋጋሚ ተጠይቀው አሻፈረኝ ብለው እስላማዊው ፍርድ ቤት እስር በይኖባቸው ነበር፡፡ ጉዳዩ አቡጃ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዘልቆ ነበር፡፡ በወቅቱም 57ቱ ሚስቶቻቸው ፍርድቤት ቀርበው «ማሳባን ያገባነው ወደንና ፈቅደን ነው፤ ደግሞም መልካም ባልና አባት ነው» የሚል ምስክርነታቸውን በመስጠታቸው ከእስር መለቀቃቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡

«ማናችሁም ምንም ብትሉ በሕይወት እስካለሁ ድረስ ማግባቴን እቀጥላለሁ» በሚል ንግግራቸው ይታወቁ የነበሩት ማሳባ ድርጊታቸውን ለሚቃወሟቸውም «እናንተ በፈጣሪያችሁ ላይ ጦርነት ያወጃችሁ ናችሁና ከእኔ ወግዱ» በማለት ነበር የሚመልሱላቸው፡፡ ሞት ቀደማቸው እንጂ በቅርቡም ሁለት ሴቶች ለማግባት እቅድ እንደነበራቸው የናይጄሪያ ዜና አገልግሎት ዘገባ አመልክቷል፡፡

 

አንዱዓለም አሰፋ

 

Published in መዝናኛ

 

ትዝብት

አሁን አሁን በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ ወጣ ብሎ ትራንስፖርት ማግኘትም ሆነ ከትራፊክ መጨናነቅ ነፃ የሆነ መንገድ ዘበት እየሆነ ነው፡፡ እንዲውም በተገላቢጦሽ እየሆነ ያለው ካለሰልፍ ትራንስፖርት ካገኙ መንገዱም ነፃ ሆኖ ካሰቡበት በፍጥነት ከደረሱ «ዛሬ ምንድነው» ብለው ምክንያት ይፈልጋሉ፡፡ ይህን ማንሳቴ ከትራንስፖርት ጋር በተያያዘ እኔም የገጠመኝን ላካፍላችሁ፡፡ ባለፈው ዓርብ ነው፡፡ ከቤቴ በግምት ስምንት ሰዓት ተኩል አካባቢ ነው የወጣሁት፡፡ ትራንስፖርት የምይዝበት ቦታ ስደርስ አንድ ቢጫ የከተማ አውቶቡስ ቆሞ አገኘሁ፡፡ አሊያንስ የተባለ አዲስ ባለቢጫ ቀለም አውቶቡስ ነው፡፡ በወጣሁበት ሰዓት ትራንስፖርት ማግኘቴ አስደሰተኝ፡፡ የነበረው ተሳፋሪም ጥቂት ነው፡፡ መቀመጫ ወንበርም አገኘሁ፡፡ ባሱ በተሳፋሪ ሳይጨናነቅ ነፃ በሆነ መንገድ ልንጓዝ በመሆኑ ደስ አለኝ፡፡ አውቶብሱም አዲስ ነው፡፡ አውቶቡሱን ያየሁትም የተጠቀምኩበትም ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ለከተማችን አዲስ የትራንስፖርት አገልግሎት ነው፡፡

ጉዟችን ከጀሞ ፒያሳ ነበር፡፡ ለጉዞውም አራት ብር ከፍለናል፡፡ አውቶቡሱም ለተወሰነ ጊዜ ተሳፋሪዎችን ጠብቆ ተንቀሳቀሰ፡፡ ከዚህ በኋላ የተፈጠረው አጋጣሚ የሚገርም ነበር፡፡ እርሱን ላካፍላችሁ፡፡ የተሳፈርንበት አውቶቡስ የተወሰነ ኪሎ ሜትር ይዞን እንደሄደ ቆመ፡፡ ምንድነው ሲባል የተሳፋሪ መግቢያና መውጫ በሮች በደንብ ባለመግጠማቸው እንደሆነ በዕድሜ ጠና ያሉት የአውቶቡሱ ሾፌር ነገሩን፡፡ በሩን እየዘጉና እየከፈቱ ሞተር ለማስነሳት ቢሞክሩ አልሆነም፡፡ ተሳፋሪው ቢቸግረው የራሱን ግምት መስጠት ጀመረ፡፡ በአጋጣሚ በዕለቱ ታቦት ይገባ ስለነበር መንገድ በመዘጋቱ በሌላ አቅጣጫ ለመሄድ ወደኋላ ተመልሶ ስለነበር፡፡ መመለሱ ይሆን? የሚልና ከአውቶቡሱ የውስጥ አናት ላይ ለአየር ማስገቢያ የተገጠመው በመከፈቱ ይሆን? በሚልም ለመዝጋት ሙከራ አደረጉ፡፡ በበሩ አካባቢ ያሉ ነገሮችንም በመነካካት ለማገዝ ጥረት አደረጉ፡፡ አልሆነም፡፡ተሳፋሪ «ወይ በሌላ ሸኙን ወይ ብራችንን መልሱልን» ብሎ ጠየቀ፡፡ መልስ የለም፡፡ ሾፌርና ትኬት ቆራጭ መፍትሔ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡

በአጋጣሚ ሌላ ባስ የያዘ የሥራ ባለደረባቸው መጥቶ አንዳንድ ነገሮች ነካክቶ ባሱ ተንቀሳቀሰ፡፡ከተሳፋሪው መካከል አንዳንዱ የሾፌሩ ችግር ይሆናል ብሎ አስተያየት ይሰጣል፡፡ ሌላው ደግሞ መጀመሪያ ስልጠና ማግኘት እንደነበረባቸውና ለሀገራችን ተስማሚ ያልሆነ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደማያስፈልግ አስተያየት ይሰጣል፡፡ ይሰጥ የነበረው ሃሳብ ሳይቋጭ አውቶቡሱ እንደገና ቆመ፡፡ እንዳጋጣሚ መጀመሪያ ነካከቶ ሞተሩን ያስነሳው የሥራ ባልደረባቸው ተከትሎን ስለነበር ነገሩ ግራ ገባን፡፡ አውቶብሱ ችግር እንዳለበት የሚያውቁና በተሳፋሪው እንደሚቀልዱ አስመሰለባቸው፡፡ አውቶቡሱን በድጋሚ ማስነሳት አልተቻለም፡፡ተሳፋሪው ዕርዳታ ያደረገውን ውሰደን ብሎ ቢጠይቅም «አይመለከተኝም፡፡ እቀጣለሁ» አለ፡፡ ከተሳፋሪው መካከል ወደሚመለከተው ስልክ ደውሎ እንዲያሳውቅላቸው የስልክ ቁጥር ጠይቆ ደወለ፡፡ መፍትሔ የሚሰጥ አካል አልተገኘም፡፡ ተሳፋሪው በድጋሚ «ገንዘባችንን መልሱልን» የሚል ጥያቄ አነሳ፡፡ ትኬት ቆራጯ እንደማይመለስ እቅጩን ተናገረች፡፡ ተሳፋሪ ጮኸ፡፡ ወደኋላም ወደፊትም መመለስ አልተቻለም፡፡ በአንድ ቦታ ከሁለት ሰዓት በላይ ታገትን፡፡ «አጋች ታጋች» የሚለው ድራማ ትዝ አለኝ፡፡

ሾፌሩ እንደገና ወደአውቶቡሱ ተመልሰው አንዳንድ ነገሮችን ነካኩ፡፡ ከጥቂት ሙከራ በኋላ አውቶቡሱን አስነስተው ይዘውን ተጓዙ፡፡ እዚህ ላይም የሚገርመው ተሳፋሪው ይቅርታ አልተጠየቀም፡፡ ላጠፉት ጊዜም ማካካሻ በፍጥነት ለማድረስ ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ ይልቁንም በየፌርማታው እየጫኑ ሥራቸውን ሠሩ፡፡ ከሁለት ሰዓት ተኩል ጉዞ በኋላ ፒያሳ አደረሱን፡፡ «ደበኛ ንጉሥ ነው» የሚለው በእነርሱ አገልግሎት እንዴት እንደሚታይ ትኬት ቆራጯንና ሾፌሩን ጠየቅኳቸው «ምን እናድርግ ሥራችንን ካልሠራን እንቀጣለን» በማለት ነበር ምላሽ የሰጡኝ፡፡ አፌን ከመያዝ በስተቀር ሌላ አማራጭ አልነበረኝም፡፡ ተገልጋይ መቼ ይሆን የሚከበረው?

 

ለምለም መንግሥቱ

 

 

Published in መዝናኛ
Friday, 03 February 2017 18:14

ሰዓቱንም እንደብሩ

 

በልዩ ልዩ ቦታ ተቀጥረው የሚያገለግሉ ሁሉ የሥራቸው ዋጋ እንዲከፈላቸው መደረጉ ተገቢ እንደመሆኑ የሠራ የድካሙን ዋጋ ያገኛል የድካሜ ዋጋ ይከፈለኝ ብሎ በወር መጨረሻ የሚጠይቅና አንድ ሳንቲም ሳትቀር በጥንቃቄ ቆጥሮ እንደሚቀበለው ሁሉ የሥራ ሰዓቱን አክብሮ መግባቱንም ሌላው ባይቆጣጠረው እንኳን ራሱ ራሱን ሊቆጣጠር ይገባል:: የመግቢያውን ሰዓት አክብሮ ሥራ የገባ ሁሉ በሥራ ገበታው ላይ ሆኖ ብዙ ውጤት ያስገኛል ብለን ሙሉ በሙሉ ባናረጋግጥም (ከገባ በኋላ ሊለግም ይችላልና )ጥሩ ተቆጣጣሪ ገምጋሚ ካገኘ ብዙ ሊያመርት እንደሚችል ይታመናል:: በወር ውስጥ በአማካይ ብሔራዊ በዓላት ሳይደመሩ 6 ቀን ሙሉ ሥራ አይሠራም (ይህም ማለት በ 28 ቀን ውስጥ 4 ዕሁድና 4 ግማሽ ቅዳሜ የሥራ ቦታዎች ዝግ ስለሚሆኑ ነው።)

በየቀኑ 30 ደቂቃ ዘግይቶ ሚገባ ሰው በ 24 የሥራ ቀኖች ስናሰላው በወር 12ሰዓት ሙሉ ሊያበረክት የሚገባውን አለማበርከቱን እንገነዘባለን በዓመት ሲሆን 244 ሰዓት አገልግሎት አለመስጠቱን ያስረዳል። ይህም ማለት በዓመት ውስጥ ለ16 ቀናት ከሥራ ገበታው ተለይቶል ማለት ሲሆን፤ በሙላው የአገልግሎት ዘመኑ ሲሰላም የትየለሌ ነው:: በዚህ ላይ የዓመት ፍቃድ፤ የሠርግ ፤የወሊድ፤ የማህበር ፤የህመም ፤የኀዘን ፤የድንገተኛ ጥሪ ፈቃዶች ሲጨመሩ ሰዓት ተደምሮና ቀን ተቆጥሮ ለሚከፈል የደመወዝ ቀን ተቆጥሮ የማበረክተው አገልግሎት በትክክል ነው ወይ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል።

በብዙ መስሪያ ቤቶችና ድርጅቶች የመግቢያ ሰዓት ላይ ቆም ብሎ ለሚመለከት ታዛቢ አገባቡ እጅግ የተንጠባጠበ ከመሆኑም በቀር ብዙ የዘገየ በመሆኑ ማንም ለመግባት ሲጣደፍ አይታይም ይህ የሚመለከተው የመስሪያ ቤቱን ወይም የድርጅቱን የቁጥጥር ልልነት ነው፡፡ በአንፃሩ በመውጪያ ሰዓት ላይ ያለውን ግፊያና ትርምስ የተመለከተ ሲወጣ እንዲህ ከተቻኮለ ሲገባም እንዲያ ቢሆን ብሎ ምኞቱን ይገልጣል፤ ስለሆነም የሥራ ሰዓትን በማክበር ረገድ ሁሉም ሊያስብበት የሚገባው ከመሆኑም በቀር እንዳወጣጡ ለአገባቡም ብንጣደፍ መልካም ይሆናል፤ አለዚያም ከብሩም በወሩ መጨረሻ ማስቀነስ ይመጣል።

(የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ መስከረም 13ቀን 1976 .ም ከፋንታሁን ኃይሌ)

 

ብሌን ገብሩ

Published in መዝናኛ
Friday, 03 February 2017 18:05

ሰብሎችንም እንደዕፅዋት

 

የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚው የአቶ ታለጌታ የምርምር ውጤት በሠርቶ ማሣ ላይ፤

 

እንግዳችን አቶ ታለጌታ ልዑል በምርምር ሥራ የአንድ ጎልማሳ ዕድሜ አሳልፈዋል፡፡ «አይሆንም፣ አይቻልም» የሚለው ሃሳብ በእርሳቸው ዘንድ ቦታ የለውም፡፡ ወደኋላ መለስ ብለው እንዳጫወቱኝ ተወልደው ባደጉበት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ መንዝና ጊሼ ወረዳ በመሃልሜዳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት ተማሪ ሆነው ሥነህይወት «ባዮሎጂ» እና ኬሚስትሪ ሲማሩ በአዕምሯቸው ውስጥ የተለያዩ ጥያቄዎች ይመላለሱ ነበር፡፡ከጥያቄዎቹም መካከል «ጥርስ ከተነቀለ በኋላ ለምን መልሶ አይተከልምየሚለው አንዱ ነበር፡፡

በአጋጣሚም በኬኒያ ሀገር «ዴንታል ቴራፒ» በሚባለው የትምህርት ዘርፍ ለመማር ዕድሉን አገኙ፡፡ መልካም አጋጣሚው ቢፈጠርም ለጥያቄያቸው መልስ አላገኙለትም፡፡ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋርም አላስማማቸውም፡፡ ሃሳባቸውን እንዳልተረዷቸውም ይገነዘባሉ፡፡ በተለያየ ምክንያት ሰው ጥርሱ ሲወልቅ ሰው ሠራሽ ጥርስ ከሚያስተክል የወለቀውን መልሶ መትከል ለምን አይቻልም? የሚል ጥያቄ ነበራቸው፡፡ ይቻላል የሚለውን ለማሳየትም ሁለት ጥርሶቻቸውን አውልቀው እንደገና በመትከል በራሳቸው ላይ ተግባራዊ ሙከራ አድርገው እወነታውን እስከማረጋገጥ ደርሰዋል፡፡ ነቅለው የተከሏቸው ሁለት የፊት ጥርሶቻቸው 24ዓመት እንደሆ ናቸውና ችግር እንዳልገጠማቸውም ያስረዳሉ፡፡

«በጤናው ዘርፍ ሳይንሱ አዲስ ነገር ስላላስገኘልኝ በተማርኩት የጥርስ ህክምና ሙያ አልገፋሁበትም» የሚሉት አቶ ታለጌታ ፊታቸውን ወደ «የጀነቲክ ምህንድስና ሳይንስ»አዞሩ፡፡ ከልጅነታቸው ጀምረው የሚያወቁት የግብርና ሥራ እስከዛሬ አለማደጉ ቁጭት እንዳሳደ ረባቸውም ያስታውሳሉ፡፡ የሥራውን አድካሚነት ስለሚያውቁት የገበሬውን ድካም የሚቀንስ ነገር መፈጠር ከልጅነት ጀምሮ የሚያስቡት ነበር፡፡ በአዕምሯቸው ሲብላላ የነበረው ፍላጎት ጊዜው ደርሶ «እጅህ ከምን» ለመባል በቅተው በሠርቶ ማሳያ ማሣ ላይ የሚታይ የምርምር ሥራ ውጤት አበርክተዋል፡፡

ስለምርምር ግኝታቸውም እንዳስረዱት በየዓመቱ በሬ ጠምዶ የሚከናወን የእርሻ ሥራን የሚያስቀር ነው፡፡ገበሬው አንዴ ባረሰው መሬት ላይ የዘራው ሰብል ሁለት ዓመትና ከዚያ በላይም ለሆነ ጊዜ ምርት ለመሰብሰብ የሚያስችል ሲሆን፤ የምርምር ዘዴው ሰብሉ እንዳያረጅ ወይም እንዳይሞት የሚያደርግ ነው፡፡ ገበሬው አንዴ ባዘጋጀው መሬት ላይ የዘራው ሰብል እንደዛፍ ቅርጫፍ እያበጀ ምርት ይሰጠዋል፡፡ የምርምር ግኝቱ ሰብሎችም እንደእፅዋት ለረጅም ጊዜ ምርት እንዲሰጡ ማስቻል ነው፡፡ አንዴ ከተተከለ ዛፍ ላይ በየዓመቱ ምርት መሰብሰብ እንደማለት ነው፡፡

የዚህ የአስተራረስ ዘዴ ዘርፈብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል፡፡ አርሶአደሩ በየዓመቱ በሬ ጠምዶ መሬት ከማረስ በማስቀረት ብቻ አይወሰንም፡፡ ለእርሻ የሚሆን በሬም ሆነ በእርሻ ሥራ የሚያግዘው ለሌለው ገበሬ ጥሩ አማራጭ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ አርሶአደሩ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን ለመሥራትም ጊዜ ለማገኘት እንደሚረዳውም ይገልጻሉ፡፡ የምርምር ዘዴው በማሽላና በዘንጋዳ ዝርያዎች ነው የተሞከረው፡፡

በኦሮሚያ ክልል በአምቦ ፤ በአማራ ክልል ደግሞ በሰሜን ሸዋ በቆላማ አካባቢዎች በአምስት መቶ ካሬ ሜትር ላይ ነው ሠርቶ ማሳያው የተከናወነው፡፡ በሠርቶ ማሳያው ላይ አንዴ የተዘራው ዘርም ቅርንጫፍ እያበጀ ምርት በመስጠት ስምንት ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ ጤፍና ባቄላ ላይም ሙከራ እየተደረገ ነው፡፡ ሁለቱ ሰብሎች የበጋ ፀሐይን መቋቋም ስለማይችሉ ምርምሩ ሠፊ ጊዜ ይፈልጋል፡፡

በዚህ መንገድ ያልተቋረጠ ምርት ለመሰ ብሰብ ግን በቂ የሆነ ውሃ መገኘት አለበት፡፡ ውሃ ሳይቋረጥ ለማግኘትም ዘዴው ቀላል እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ የክረምቱን ውሃ ሰብስቦ ለተከታታይ ጊዜ ለመጠቀም የሚያስችል መሣሪያም በእጃቸው መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡ የውሃ ማጠራቀሚ ያውንም ለመሥራት ቀላል መላ ዘይደዋል፡፡

አቶ ታለጌታ የምርምር ሥራቸው በሠርቶ ማሳያ ደረጃ እስኪደርስ ላደረጉት ጥረት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሁለት መቶ ሺህ ብር ድጋፍ አድርጎላቸዋል፡፡ በኋላም ሚኒስቴሩ በቅርቡ ባካሄደው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሽልማት በምርምር ዘርፍ የወርቅ ሜዳሊያ በመሸለም እውቅና ሰጥቷቸዋል፡፡

ከልጅነት እስከ እውቀት በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ ያለፈው የምርምር ሥራ እውቅና በማግኘቱ ለሽልማቱ ልዩ ግምት ይሰጣሉ፡፡ እርሳቸው እንዳሉት ምርምራቸው በሌሎች ተቀባይነት እንዲያገኝ ብዙ ደክመዋል፡፡ በምርምር ዘርፍ በሚገኙትንም ሆነ በተለያዩ አካላት ድጋፍ ለማግኘት ባለማቻላቸው እስከዛሬ እንደቆየ ይናገራሉ፡፡ የምርምር ሥራቸው ለውድድር ቀርቦ ከአስራአምስት ጊዜ በላይ የወደቀበትንም ጊዜ ያስታውሳሉ፡፡ ተስፋ ሳይቆርጡ ላለፉት አርባ ዓመታት በምርምር ውስጥ እንደቆዩና ዛሬ ተስፋ ማየታቸውን ደስታ በተሞላ ስሜት ይናገራሉ፡፡

በሠርቶ ማሳያ ላይ ያሳዩት የምርምር ውጤት ወደገበሬው ሰፍቶ ወደተግባር ያልተሸጋገረበትን ምክንያት እንዳስረዱት፤ እውቅና ለማግኘት የወሰደው ሂደት ረጅም መሆኑ፣የገንዘብ ድጋፍ ማጣት፣በአጠቃላይ በሃሳብም ሆነ የተለያዩ ድጋፎችን ባለማግኘታቸው ምርምራቸው ከሠርቶ ማሳያው እንዳያልፍ አድርጎታል፡፡

አቶ ታለጌታ በምርምሩ ተተኪዎችን ለማፍራትም ወደኋላ አላሉም፡፡ በአሁኑ ጊዜ አራት ባለሙያዎች ከእርሳቸው ጋር እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ አራቱም በፍላጎት እያገዟቸው እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ አበረዋቸው ከሚሠሩት መካከልም አቶ ደረጀ አውግቸው በተለያየ የትምህርት ዘርፍ ውስጥ ያለፉ ባለሙያ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ በመጀመሪያ ዲግሪ በደን፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ የማህበረሰብ ሳይንስ ነው የተማሩት፡፡ በተማሩት ሙያም በተለያዩ ተቋማት ውስጥ አገልግለዋል፡፡

ላለፉት አምስት ዓመታት ግን ከአቶ ታለጌታ ጋር በምርምር ሥራውን አብረው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ «እኔ በሙያዬ ገበሬው ጋር ብዙ ሠርቻለሁ፡፡ የገበሬው ችግር በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፡፡ 85 በመቶ የሚሆን ገበሬ ይዘን ውጤታማ አልሆንም፡፡ ለምን ብለን እራሳቸንን መጠየቅ አለብን፡፡ አሜሪካን ሀገር ከአምስት በመቶ በታች የሆነ ገበሬ ይዘው ውጤታማ እየሆኑ ነው ለምን? ብለን መፈተሽ ይኖርብናል፡፡ እንዲህ ያለው ችግር ፈች የሆነ ምርምር በሥራ ላይ አለመዋሉ ያስቆጫ ል» ይላሉ፡፡

የአቶ ታለጌታን የምርምር ግኝት ለመረዳት አብሮ መሥራት ይገባል ያሉት አቶ ደረጀ እርሳቸው አብረዋቸው በመሥራታቸው እውቀት እንዳገኙበት ይገልጻሉ፡፡ የምርምር ውጤቱንም በሦስት መንገድ በመግለጽ ያብራራሉ፡፡ አንዱ የገበሬውን ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መሬቱ ዓመቱን ሙሉ በአረንጓዴ ሲሸፈን ለአየርንብረት ለውጥ መጠበቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ የአፈር መሸርሸርንና የውሃ ትነትን ማስቀረትም ሌላው ጥቅሙ እንደሆነ ይገለጻሉ፡፡

 

ለምለም መንግሥቱ

 

 

 

Published in ማህበራዊ

 

አመልካች፡- አቶ እንደልቡ ሣህሉ (ስማቸው የተቀየረ)

ተጠሪ፡- አቶ አላምረው ክብነህ (ስማቸው የተቀየረ)

አመልካች ፅፈው ባቀረቡት የክስ ማመልከቻ ተጠሪ በስማቸው ተመዝግቦ የሚታወቀውን የግል ቤታቸውን በመያዣነት አስይዘው ብር 12,000.00 (አሥራ ሁለት ሺ) ተበድረው ቤቱን እንዳስረከቧቸው፤ በስምምነቱ ወቅት የማይንቀሳቀስ ንብረት መሸጥና መለወጥ ችግር ስለነበር ገንዘቡ የ10 ዓመት መክፈያ ጊዜ ተወስኖለት ቀነ ገደቡ ማብቃቱን፤ ነገር ግን በብድርና የዋስትና ውል ቤትን መሸጥና መለወጥ በመንግሥት ሲፈቀድ፤ አመልካች ብር 5,000.00 (አምስት ሺህ ብር) ለተጠሪ በመጨመር ከወሰዱት ብር 12,000.00 ጋር ተደምሮ ብር 17,000.00 (አሥራ ሰባት ሺህ ብር) ቤቱን በሽያጭ ለማስተላለፍ ተጠሪ ውል መፈረማቸውን፤ የቤቱን የዕድሳት ወጪዎችም አመልካች እንዲሸፍኑ፤ ተጠሪ ፈቃዳቸውን በውሉ የገለጹላቸው ሆኖ ተጠሪ ከወሰዱት የቤቱ መያዣ ብድር ጋር የእድሳት ወጪ ሲደመር ብር 18,787 (አሥራ ስምንት ሺህ ሰባት መቶ ሰማንያ ሰባት ብር) መሆኑን፤ የቤት ሽያጩም በመንግሥት መፈቀዱን ዘርዝረው ተጠሪ በስምምነቱ መሠረት የብድሩን ገንዘብ በወቅቱ ካለመመለሳቸውም በላይ የቤቱን ስመንብረት በሽያጭ ለማስተላለፍ በአማራጭ የገቡትን ግዴታ በወቅቱ ስላልፈፀሙላቸው አመልካች ብር 5,000.00 (አምስት ሺህ) ለተጠሪ ጨምረውላቸው የቤቱ ስም ለአመልካች እንዲዛወር ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ ለማስረጃነትም የጽሑፍና የሰው ምስክሮችን ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡

የአሁኑ አመልካች የክስ ማመልከቻና ማስረጃ ለተጠሪ እንዲደርስ ተደርጎ በጥሪው መሠረት ባለመቅረባቸው ጉዳዩ በሌሉበት እንዲታይ ተደርጓል፡፡ ፍርድ ቤቱም የአመልካችን ክስና ማስረጃ መርምሮ በአመልካችና በተጠሪ መካከል የተደረገ ውል የመያዣ ውል ሳይሆን የወለድ አገድ ውል ነው፣ ውሉ በተደረገበት ወቅት የወለድ አገድ ግንኙነት የሚገዛው በአዋጅ ቁጥር 47/67 ስለነበር ይኸው አዋጅ የወለድ አገድ ውሉን የሚከለክል በመሆኑ ውሉ ሕገወጥ ስለሆነ ፈራሽ ነው፤ ተዋዋዮች ወደ ነበሩበት ይመለሱ፤ ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ቤት አመልካች ያስረክቡ፤ ተጠሪ ከአመልካች የወሰዱትን ገንዘብና የቤት ማደሻ ብር በገቡት ውል መሠረት ለከሳሽ ይክፈሉ በማለት ወስኗል፡፡ ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤትም የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ አጽንቶታል፡፡ ይሁን እንጂ በጉዳዩ ያልተደሰቱት አመልካች ቅሬታቸውን ለሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበዋል፡፡

አመልካች የበታች ፍ/ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት አለበት የሚሉባቸውን ምክንያቶች ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡

የበታች ፍ/ቤቶቹ ተጠሪ ቀርበው ባልተከራ ከሩበት እና የተጠያቂ ዳኝነት በሌለበት ሁኔታ ቤት እንዲረከቡ መወሰናቸው ያላግባብ በመሆኑ ውሳኔው ተሽሮ በውል ያገኙት መብት ተጠብቆ እንዲወሰ ንላቸው በመጠየቃቸው የአመልካች የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ በጉዳዩ ከተጠየቀው ዳኝነት በተለየ ሁኔታ የተሰጠውን ውሳኔ የህግ አግባብነት ለማጣራት ተጠሪ እንዲቀርብ ተደርጎ ተጠሪው መልሳቸውን በፅሑፍ አቅርበዋል፡፡

ይዘቱም ፍ/ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የሌለበት፣ የፍ//1815 ድንጋጌን ያገናዘበ፣ የአመልካች ጥያቄ ግን በፍ//2851 ድንጋጌ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ዘርዝረው የበታች ፍ/ቤቶች ውስጥ ሊፀና ይገባል በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

የሰበር ችሎቱ ይህንኑ ክርክር አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ፡-

1/ የበታች ፍ/ቤቶች አመልካች ከጠየቁት ዳኝነት በተለየ ሁኔታ የሰጡት ውሳኔ ተገቢ መሆኑንና ያለመሆኑን፤

2/ የአመልካች የዳኝነት ጥያቄ የክስ ምክንያት አለው ወይስ የለውም? የሚሉትን ጭብጦች በመመርመር፡-

አመልካች ከተጠሪ ጋር ተደርጓል በሚሉት ስምምነት አከራካሪውን ቤት ተረክበው በይዞታቸው ስር አድርገው እየተጠቀሙበት የሚገኙ መሆኑን ገልጸው የሚከራከሩ ሲሆን፣ የጠየቁት ዳኝነትም ቀሪውን ብር ለተጠሪ ጨምረው የቤቱ ስመ ንብረት እንዲዛወርላቸው ይወስንላቸው ዘንድ ነው፡፡ ይህንኑ የአመልካች የዳኝነት ጥያቄ የአሁኑ ተጠሪ ፍ/ቤት ቀርበው ከስር ያልተከራከሩበት ሆኖ የስር ፍ/ቤት ግን የውሉን ህጋዊነት በራሱ ጊዜ በማንሳት ሕገወጥ ነው ወደሚለው ድምዳሜ ደርሶ ውሉ ፈራሽ ነው በማለት ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ቤት አመልካች ለተጠሪ ሊያስረክቡ ይገባል ሲል ወስኗል፡፡ ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው የስር ፍ/ቤት ውሳኔ የሰጠው የአሁኑ አመልካች በግልጽ ባላመለከቱት እና ባልጠየቁት ዳኝነት ላይ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ደግሞ በፍ////182/2/ ድንጋጌ ሥር የተመለከተውን የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የዳኝነት አሰጣጥ የስልጣን አድማስ በግልጽ የሚፃረር ነው፡፡ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤትም በይግባኝ ሰሚነቱ ስልጣን የስር ፍ/ቤትን የውሳኔ አሰጣጥ ማረም ሲገባው በተመሳሳይ ምክንያት ተቀብሎ መፅናቱ የዳኝነት አሰጣጥ ሥርዓቱን ያላገናዘበ ነው፡፡ የስር ፍ/ቤት ስለውሉ ሕጋዊነት ክርክር ባልተነሳበት ሁኔታ በራሱ ጊዜ ማንሳቱም የክርክር አመራር ስርዓቱ በሚፈቅድለት ሁኔታ አይደለም፡፡ ተጠሪ በስር ፍ/ቤት ሳይቀርቡ ጉዳዩ በሌሉበት ታይቶ ከተወሰነ በኋላ አሁን በሰበር ችሎት ያቀረቡት ክርክር ሥነ-ሥርዓታዊ የይደለም፡፡ ተጠሪ በስር ፍ/ቤት ሳይቀርቡ ታይቶ በተሰጠው ውሳኔ ለበላይ ፍ/ቤት ሊያቀርቡ የሚችሉት ክርክር ከስር ክስ ተያይዘው የቀረቡትን የከሳሽን ማስረጃዎች አግባብነት፣ ተቀባይነት እና ጥንካሬ ያገናዘበ መሆን ያለመሆኑን መሠረት በማድረግ ብቻ የተወሰነ ነው፡፡ ስለሆነም ተጠሪ በዚሁ የክርክር ደረጃ ያነሱት ክርክር ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ከላይ የተጠቀሰውን የሥነ-ሥርዓት ሕግ ድንጋጌ ያላገናዘበ በመሆኑ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በሁለተኛው ጭብጥም በመጀመሪያው ጭብጥ ላይ እንደተገለጸው የአመልካች የዳኝነት ጥያቄ አግባብነት በመመርመር ውሳኔ መስጠት እየተገባው ከተጠየቀው ዳኝነት በተለየ ሁኔታ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ የአመልካች ጥያቄ ተገቢነት ያለው መሆን ያለመሆኑን፤ የስር ፍ/ቤት በጭብጥነት ይዞ በሕጉ አግባብ የሰጠው ውሳኔ ባይኖርም ከተጠየቀው ዳኝነት ይዘት በሰበር ችሎቱ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ጉዳይ ከተሰጠው ሕግ ትርጓሜና ከፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ዓላማ አኳያ ሲታይ በዚህ ችሎት ለጉዳዩ እልባት መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህ መሠረት የአመልካች የዳኝነት ጥያቄ የሚያስከስስ ሊሆን ይችላል አይችልም? የሚለው ነጥብ ምላሽ የሚያስፈልገው ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ከአመልካች ክስና ክርክር ማረጋገጥ የተቻለው ከተጠሪ ጋር በተደረገው ስምምነት ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ቤት አመልካች ተረክበው ለረጅም ጊዜያት በይዞታቸው ሥር አድርገው የሚገኙ መሆኑን፤ ቤቱን የሚመለከቱ አስፈላጊ ሰነዶችም በተጠሪ እጅ ይገኛሉ ተብሎ በክሱ አለመገለጹንና የዳኝነት ጥያቄ ያልቀረበበት መሆኑን በተጠሪ በኩል መፈፀም አለበት የተባለው የቤቱ ስመንብረት መዞር ብቻ መሆኑን ነው፡፡ የስም ዝውውር ተግባር የሚፈፀመው በመንግሥት አስተዳደር ክፍል ፊት እንጂ ሻጭ ነው የተባለው ወገን ሊፈፅም ይገባል ተብሎ ከሕግ ወይም ከውል ያመነጫል ሊባል የማይችል ግዴታ ነው፡፡ የስም ዝውውር ጥያቄ የሚስተናገደው የባለሀብትነት የምስክር ወረቀት በሚሰጥ የመንግሥት አስተዳደር አካል ገዢው ውልና አስፈላጊ ሠነዶች ይዞ ሲቀርብ እንጂ በፍ/ቤት ክስ ቀርቦ ዳኝነት የሚሰጥበት አይደለም፡፡ አንድ ክስ ሊቀርብ የሚገባው የክስ ምክንያት ሲኖረው ሲሆን፤ የክስ ምክንያትም ተከሳሽ ለከሳሽ ሊፈፅመው የሚባው ግዴታ መኖሩ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለውን ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት የሚችልበት ሁኔታ ስለመኖር ሲረጋገጥ የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህ መሠረት አመልካች ተጠሪ የስም ዝውውሩን እንዲፈፅሙ ይወሰንልኝ ብለው ዳኝነት መጠየቃቸው በተጠሪ በኩል ሊፈፀም የሚገባ የሕግ ወይም የውል ግዴታ የሌለ መሆኑን ስለሚያሳይ በፍ/////. 231/1/ሀ ፍሬ ነገሩ የማያስከስስ ነው ተብሎ መወሰን ያለበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡

 

ውሳኔ

1. በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ተሰጥቶ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የፀናው ውሳኔ በፍ/////. 248/1/ መሠረት ተሽሯል፡፡

2. አመልካች የስም ዝውውር ጥያቄ ታይቶ ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት ጠይቀው እያለ ከተጠየቀው ዳኝነት በተለየ ሁኔታ ውሉ ሕገወጥ ነው ተብሎ ቤቱን እንዳያስረክቡ መሆኑ የዳኝነት አሰጣጥ ሥርዓትን የተከተለ አይደለም ብለናል፡፡

3. የአመልካች የስም ይዛወርልኝ ጥያቄ የሚያስከስስ ምክንያት የለውም ብለናል፡፡

4. ግራ ቀኙ ወጪና ኪሣራ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

5. መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

አያሌው ንጉሤ

 

 

Published in ፖለቲካ

 

ከአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ነፃነታቸውን የተቀዳጁ 32 የአፍሪካ አገራት እ..አ ግንቦት 25 ቀን 1963 የአህጉሪቱን ዜጎች ከቅኝ ግዛት ለማላቀቅና አንድነታቸውን ለማጠናከር በማሰብ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (Organization for African Unity - OAU)ን መሰረቱ፡፡ ቀሪዎቹ 21 አገራት ቀስ በቀስ ኅብረቱን እየተቀላቀሉ በመምጣታቸው የአባል አገራት ቁጥር 53 ደርሷል፤ እ..አ ሐምሌ 9 ቀን 2011 ደግሞ ደቡብ ሱዳን 54ኛዋ የኅብረቱ አባል አገር በመሆን ተመዘገበች፡፡ በ28ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ውሳኔ መሠረት ከ33 ዓመታት በኋላ ኅብረቱን በድጋሚ የተቀላቀለችው ሞሮኮ የኅብረቱን አባል አገራት ቁጥር 55 አድርሳዋለች፡፡

ድርጅቱም ዋና መቀመጫውን የአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን የመላ ጥቁር ህዝቦች የፅናትና የጀግንነት ምሳሌ በሆነችው ኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ላይ አድርጓል። ኢትዮጵያ ከቅኝ ግዛት ያልተላቀቁ የአፍሪካ አገራት ነፃ እንዲወጡ ከማድረግ ጀምሮ መላ የአህጉሪቱ አገራት ለጋራ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና በጋራ እንዲሠሩ ግንባር ቀደም ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች፡፡

የድርጅቱን የአፍሪካዊነት ስሜትና አንድነት የማሳካት ዓላማዎችን በተሻለ ማዕቀፍ ለመፈፀም ድርጅቱ መዋቅራዊ አደረጃጀቱን በማሻሻል እኤአ በ2002 ስያሜውን ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት (African Union - AU) ቀይሯል። ህብረቱ በቅኝ ግዛት የተያዘ አገር ትኩረቱን በውስጥ ሰላም እና በእርስ በርስ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስሮች ላይ በማድረግ አህጉሪቱን የማልማትና አፍሪካዊነትን የማለምለም ጥረቱን ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡

በእኤአ 2013 ይፋ የሆነውና በ50 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የበለጸገች አፍሪካን ዕውን ለማድረግ የተዘጋጀው አጀንዳ 2063 በመባል የሚታወቀው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ፣ ኅብረቱ እየተገበራቸው ከሚገኙ መርሐ ግብሮች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ይህ የድርጊት መርሐ ግብር «አንድነት ያላት፣ የበለጸገች፣ ሰላማዊ የሆነች፣ በራሷ ዜጎች የምትመራና በዓለም አቀፍ መድረክ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነች» አፍሪካን ዕውን የማድረግ ርዕይ ያለው ሲሆን፤ እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት የሚያግዙ መነሻ መሠረቶችንም ይዟል፡፡

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ይሁን የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት በፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ በመታገዝ አፍሪካንና አፍሪካውያንን የማዋሀድ ዓላማን ሊያሳኩ በሚችሉ ትስስሮች ላይ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ በአጀንዳ 2063 ከተጠቀሱት መርሐ ግብሮች መካከል «ሁለንተናዊ አንድነት ያላትና ጠንካራ አፍሪካን መመስረት» የሚለው የመርሐ ግብሩ አንኳር ክፍል ኅብረቱ የአህጉሪቱንና የህዝቦቿን አንድነትና ውህደት ዕውን የሚያደርግና ወሳኝ ለውጥ የሚያመጣ ግብዓት እንዲተገብር ይበልጥ አስገድዶታል፡፡

በዚህም «የአፍሪካና ህዝቦቿ ውህደት እንዴት እውን ለሆን ይችላልየሚል የመነሻ ሃሳብ በመያዝ ዕቅዱን ሊያሳኩ የሚችሉ አማራጮችን ቀርበዋል። በተለይም በአፍሪካ አገራትና ዜጎች መካከል የንግድና የባህል ግንኙነት በመመስረት ሁለንተናዊ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችሉ መሆናቸውን ተጠቅሰዋል። ለመተግበርም ጅምር ጥረቶች ተደርገዋል፡፡

አህጉራዊ ውህደትንና አንድነትን በሚሰብከው በፓን አፍሪካኒዝም (Pan-Africanism) አስተሳሰብ የተቃኘው የአፍሪካ ኅብረት የአህጉሪቱን ህዝቦች አንድነት የማረጋገጥ አደራውን ከቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተረከበ ጊዜ ጀምሮ ዓላማውን ያሳካሉ ያላቸውን መርሐ-ግብሮች ነድፎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፤ እየተንቀሳቀሰም ይገኛል፡፡ ምንም እንኳ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ባያመጡም ኅብረቱ አፍሪካውያን በባህል፣ በንግድና በፖለቲካ ቁርኝት እንዲኖራቸው በርካታ የድርጊት መርሐ ግብሮችን ነድፎ ለተግባራዊነቱ መጣሩ ይነገርለታል፡፡

ይሁን እንጂ የአፍሪካ ኅብረት በአህጉሪቱ አገራት መካከል ኢኮኖሚያዊ ትስስርና ፖለቲካዊ ውህደት በመፍጠር ረገድ የተጓዘው ርቀት አዝጋሚ እንደሆነ የሚገልጹ አካላትም አልጠፉም፡፡

የአፍሪካ ሂውማኒተሪያን አክሽን ምክትል ፕሬዚዳንትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ፣ የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ይባል በነበረበት ወቅት ይዞት የነበረውን አፍሪካውያንን ከቅኝ ግዛት የማላቀቅ ዓላማን ማሳካት ቢችልም አሁን ባለው ቁመና ጉልህ የኢኮኖሚ ትስስርና የፖለቲካ ውህደት ሚናውን እየተወጣ እንዳልሆነ ያስረዳሉ፡፡ ማስረጃቸውም ኅብረቱ የአህጉሪቱን ኢኮኖሚያዊ ትስስርና ፖለቲካዊ ውህደት ለማሳካት የሚያግዙ ትልልቅ ዕርምጃዎችን ከመውሰድ ይልቅ በየወቅቱ ስብሰባዎችን በማካሄድና የውሳኔ ሃሳቦችን በማመንጨት ብቻ የተጠመደ ነው ይላሉ፡፡

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንደሚገልጹት፣ የአህጉሪቱ ክልላዊ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበራት እንቅስቃሴያቸው ደካማ ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያና ጅቡቲ በመንገድ፣ በባቡር፣ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ በመጠጥ ውሃና በወደብ አገልግሎት ሥራዎች በርካታ ተግባራትን ሲያከናውኑ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ሚናውን አልተዋጣም፡፡ እናም በቅድሚያ ክፍለ አህጉራዊ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበራት ሊጠናከሩ እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡

«የአገራቱ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በአገራቱ ጥቅም ላይ የሚወሰን ነው» የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ የኢትዮጵያን ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ትስስር በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡ «ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ትስስር ረገድ ጥሩ ሥራዎችን እየሠራች ትገኛለች፡፡ በትራንስፖርት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና በሌሎች የመሠረተ ልማት ዘርፍ ግንባታዎች ከጎረቤት አገራት ጋር ለመተሳሰር የምታደርገው ጥረት ምሳሌ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው» ይላሉ፡፡

እንደርሳቸው ማብራሪያ፣ በአፍሪካ አገራት መካከል ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር አገራቱ ሰላምና ፀጥታቸው የተጠበቀ ሊሆን ይገባል፡፡ ሰላም በሌለበት አካባቢ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራ የማይታሰብ ነው፡፡ ለአብነት ያህል ኢትዮጵያ ባለችበት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና አገሪቱን ከሌሎች አገራት ጋር የሚያገናኙ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ይስፋፉ ቢባል አስቸጋሪ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ በመሆኑም አፍሪካውያን መለያቸው ከሆነው የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ሊላቀቁ ይገባቸዋል ባይ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል የአፍሪካ አገራት እርስ በእርሳቸው የሚደያርጉት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የአውሮፓ አገራት ከሚያደርጉት የኢኮኖሚ ትስስር ጋር ሲነፃፀር እጅግ ያነሰ ስለመሆኑ ጠቅሰው ይህ ሁኔታ ካልተስተካከለ በኅብረቱ የፖለቲካ ውህደት ዓላማ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ እንደሚያደርግም ይገልጻሉ፡፡ ምክንያቱም ፖለቲካዊ ውህደት ለመፍጠር በቅድሚያ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን እውን ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፡፡

ኅብረቱን እንዲመሩ የሚመረጡት ግለሰቦች ጠንካራ ድርጅት ለመፍጠርና ለመምራት የሚያስችል ብቃት ጉዳይ ደግሞ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ የሚያነሱት ሌላው ጥያቄ ነው፡፡ ኅብረቱን የሚመሩት አካላት ያላቸው የአመራር ብቃትና ቁርጠኝነት አጠያያቂ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአፍሪካ መንግሥታት ራሳቸው ኅብረቱ ጠንካራ እንዲሆን ፍላጎት አላቸው ወይ? የሚለውን ጥያቄም በጥንቃቄ መመርመር እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ፡፡ «መንግሥታቱ ራሳቸው ያለባቸውን የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ሥራዎች በአግባቡ ሳይፈፅሙ ኅብረቱ ወደ ፊት ይራመዳል ለማለት አስቸጋሪ ነው» በማለት የአህጉሪቱ መንግሥታት ለኅብረቱ መጠናከር ቁርጠኛ ሊሆኑ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

በተጨማሪም፣ የገንዘብ ችግር ኅብረቱ ዓላማውን እንዳያሳካ መሰናክል እንደሆነበትም ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ያብራራሉ፡፡ የሚጠበቅባቸውን መዋጮ ለኅብረቱ የማይከፍሉ አባል አገራት ብዙ ናቸው። በዚህ ምክንያት በአንድ ወቅት ኅብረቱ ለሠራተኞቹ ደመወዝ መክፈል የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

ከአፍሪካ ኅብረት ይልቅ የምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) በቅርቡ በጋምቢያ የፖለቲካ ውጥረት የወሰደውን ዕርምጃ ግን አድቀዋል። አሁንም ቢሆን በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ እና በደቡብ ሱዳን እየተፈፀሙ ያሉ የፖለቲካ ቀውሶችን መፍትሔ ሳያገኙ እስከአሁን መቆየታቸውን እንዲሁም የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ሊቢያን ሲያፈራርስ ኅብረቱ ዓይቶ እንዳላየ ዝም ማለቱን የአፍሪካ ኅብረት ለፓን-አፍሪካኒዝምና ለአፍሪካ ውህደት እያበረከተው ያለው አስተዋፅኦ እጅግ ደካማ ስለመሆኑ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ ይገልጻሉ፡፡

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ስትራቴጂካዊ ጥናት ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ ፀሐዬም የአፍሪካ ኅብረት የአህጉሪቱን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስርና ውህደት በሚፈለገው መጠን አለማሳካቱን ይናገራሉ፡፡

እንደርሳቸው ገለጻ፣ የአፍሪካ ኅብረት ከቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የወረሰው የባህል፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ነፃነትን እውን የማድረግ ሚናውን በአግባቡ አልተወጣም። የአባል አገራቱን ትስስርና የአህጉሪቱን ውህደት ከማሳካት አንፃር ዘርፈ ብዙ ውስንነቶች ተስተውለውበታል፡፡ በዚህም አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረኮች የመደራደር አቅሟ እንዲጨምርና የአህጉሪቱ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች እንዲጠናከሩ ለማድረግም አቅም እንዳነሰው አስረድተዋል፡፡

አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ገዥዎች ነፃነታቸውን ከማግኘታቸው በፊት የነበሩት የፓን-አፍሪካኒዝምና የአፍሪካ ብሔርተኝነት ጽንሰ ሃሳቦች በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነቡ አለመሆናቸው ለኅብረቱ ድክመት ሌላው መነሻ ምክንያት እንደሆነም ያብራራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከቅኝ ግዛት ዘመናት በፊት በአፍሪካውያን መካከል ጠንካራ ትስስር አለመኖሩንም በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ እንደሚሉት፣ ኅብረቱ ከምዕራቡ ዓለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ነፃ አለመውጣቱ የአህጉሪቱን ትስስር እንዳያሳካ ያደረገው ሌላው ምክንያት ነው፡፡ በተለይ የኅብረቱ የሥራ ማስኬጃ በጀት ከበለጸጉ አገራት በደጋፍ የሚገኝ በመሆኑ የአህጉሪቱ ተፅዕኖ የጎላ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ «ዋነኛው የአህጉሪቱ ችግር የሆነው የሰላም እጦት ኅብረቱ የኢኮኖሚ ትስስርና የፖለቲካ ውህደት ሚናውን በአግባቡ እንዳያሳካ አድርጎታል» ይላሉ፡፡ ሉላዊነት የአህጉሪቱ ባህሎች በምዕራቡ ባህል እንዲሸፈኑ በማድረግ በኅብረቱ ሚና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩም ሌላው ችግር ነው ብለዋል፡፡

ክፍለ አህጉራዊ የባህል፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ትስስሮችን ማጠናከርና ጠንካራ የአፍሪካዊነት ስሜትን መገንባት ኅብረቱ አባል አገራቱን በኢኮኖሚ የማስተሳሰር ዓላማውን ለማሳካት በቀጣይ ሊያከናውናቸው የሚገቡ ዓበይት ተግባራት እንደሆኑም ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ ፀሐዬ ያስገነዝባሉ፡፡

ሰሞኑን በተካሄደው 28ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ የኅብረቱ ሊቀ መንበር ሆነው የተመረጡት የጊኒ ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ፣ ለጉባዔው ባደረጉት ንግግር «የአፍሪካውያንን መብቶችና ጥቅሞች የማያስከብር ኅብረት ፋይዳ የለውም» በማለት ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ህዝብ አሁንም በሰላም እጦትና በድህነት እየተፈተነ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሊቀመንበሩ፣ የአፍሪካ አገራት ያላቸው የእርስ በእርስ ትስስር ደካማ በመሆኑ የአህጉሪቱ ድምፅ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሳይቀር ችላ እተባለ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

«አፍሪካውያን ሲተባበሩ ድምፃቸው ይበልጥ ተሰሚነት ይኖረዋል» ያሉት ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ፣ አህጉሪቱን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የአገራቱ መንግሥታት በፓን አፍሪካኒዝም ስሜት በቁርጠኝነት ሊንቀሳቀሱ እንሚገባም አሳስበዋል፡፡

አፍሪካዊያን የሚፈልጉት በኢኮኖሚ የመተሳሰርና የመበልጸግ ፍላጎት ተሳክቶ ለማየት አሁንም የአፍሪካ አገራት መሪዎች ብዙ እልህ አስጨራሽ ትግል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

 

አንተነህ ቸሬ

Published in ኢኮኖሚ

 

የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የነበሩት ኢቲኔ ሺሴክዲ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ተከትሎ በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ተጨማሪ ክፍተት እንዳይፈጠር ተሰግቷል፡፡

በቀድሞዋ ዛየር በአሁኗ ኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ለዴሞክራሲ ስርዓት መስፈን በግንባር ቀደምትነት ከሚታገሉ ሰዎች መካከል አንዱ የነበሩት ሺሴክዲ፣ በብራሰልስ በህክምና ላይ እያሉ መሞታቸውን ፓርቲያቸው አስተውቋል፡፡ አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ ለሦስተኛ ዙር የምርጫ ዘመን እንዳይወዳደሩና ከስልጣን እንዲወርዱ በአገሪቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት የሽግግር ምክር ቤቱን እንዲመሩ ተመርጠው ነበር፡፡

የሺሴክዲ ሞት ዩኒየን ፎር ዴሞክራሲ ኤንድ ሶሻል ፕሮግረስ - UDPS የተባለውን ፓርቲያቸውን ሁነኛ ሰው ስለሚያሳጣው ባለፈው ታኅሣሥ ወር በአገሪቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በተደረሰው ስምምነት አፈፃፀም ላይ መሰናክል ሊፈጥር እንደሚችል ግምታቸውን እያስቀመጡ ያሉ ወገኖች በርክተዋል፡፡ ፌሊክስ የተባለው የሟቹ ሺክሴድ ልጅ በአገሪቱ ይመሠረታል ተብሎ በሚጠበቀው የጋራ መንግሥት ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ታጭቷል፡፡

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአምባገነንነታቸው የሚያውቃቸውን ሞቡቱ ሴሴ ሴኮን ጨምሮ በየወቅቱ ኮንጎን ያስተዳድሩ የነበሩ የአገሪቱን መሪዎችና ስርዓቶች በመቃወም የሚታወቁት ኢቲኔ ሺሴክዲ፣ ኅብረት ለዴሞክራሲና ማኅበራዊ ዕድገት የፖለቲካ ማኅበር ከመመስረቱ በፊት ሺሴክዲ በሞቡቱ ሴሴ ሴኮ የአስተዳደር ዘመን ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡

ኅብረት ለዴሞክራሲና ማኅበራዊ ዕድገት (UDPS) የተባለውን የፖለቲካ ማኅበር እ..አ በ1982 በመመሥረት ሂደት የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዙ ይነገርላቸዋል፡፡ ይኸው የፖለቲካ ማኅበርም በቀድሞዋ ዛየር የመጀመሪያው የተደራጀ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ እንደሆነም በታሪክ ሰፍሯል፡፡

1990ዎቹ ለአራት ጊዜያት ያህል ጠቅላይ ሚኒስትር ተብለው የተሰየሙ ቢሆንም ከሞቡቱ ሴሴ ሴኮ ጋር በነበራቸው ፖለቲካዊ ልዩነት የተነሳ በስልጣን ላይ ሊቆዩ አልቻሉም፡፡ በ2011 የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በጆሴፍ ካቢላ ተሸነፉ ቢባልም ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ምርጫው የተጭበረበረ እንደነበር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተደጋጋሚ የጤና መታወክ ገጥሟቸው እንደነበርና ባለፈው ሳምንት ለህክምና ወደ ቤልጅየም መጓዛቸውን ፓርቲያቸው አስታውቆ ነበር፡፡

 

አንተነህ ቸሬ

 

Published in ዓለም አቀፍ

ጠቅላይ ሚኒስትር ትሬዛ ሜይ ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር፤

 

የብሪታኒያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ወይዘሮ ትሬዛ ሜይ እ..አ ጥር 27 ቀን 2017 ወደ አሜሪካ ተጉዘው ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ፕሬዚዳንቱ ብሪታኒያን እንዲጎበኙ ያቀረቡላቸው ግብዣ ውዝግብ ማስነሳቱን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በስፋት እየዘገቡት ይገኛሉ፡፡

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስደተኞች እንዲሁም የሰባት አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚከለክለውን መመሪያ ካስተላለፉ በኋላ ለወትሮውም ቢሆን በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ በመጥፎ ዓይን የሚታዩት ትራምፕ የበረታ ተቃውሞና ውግዘት ገጥሟቸዋል፡፡

ይህን ተከትሎም የብሪታኒያ ዜጎችም ፕሬዚዳንቱ ብሪታኒያን እንዳይጎበኙ ሠፊ ቅስቀሳና ተቃውሞ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ የኪነ-ጥበቡን ዓለም ሰዎችን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ግለሰቦች በተቃውሞው ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙም ተዘግቧል፡፡ በ ዘጋርዲያን ላይ የሰፈረው ዘገባ እንደሚያመለክተው እነዚህ ታዋቂ ግለሰቦች በአገሪቱ ታሪክ ግዙፍ የተባለውን የተቃውሞ ሰልፍ ሊያካሂዱ እየተዘጋጁ ይገኛሉ፡፡ ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተውጣጡ 90 የሚሆኑ ግለሰቦች ለዘጋርዲያን በላኩት ደብዳቤ የፕሬዚዳንቱ መመሪያዎችና ተግባራት አሜሪካውያንን ብሎም ዓለምን ለመከፋፈል ያለሙ አደገኛ ፖሊሲዎች እንደሆኑ አመልክተው፣ በጋራ ትብብር አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎችን በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ለማሳተፍ ማቀዳቸውንም ገልጸዋል፡፡

ግለሰቦቹ በላኩት ደብዳቤ ዶናልድ ትራምፕን ከመቃወም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ትሬዛ ሜይ«የፕሬዚዳንቱን አጀንዳዎች ይደግፋሉ» በማለት የኮነኗቸው ሲሆን «እንዲህ ዓይነቱ ፍፁም ተገቢ ያልሆነ ጉብኝት በብሪታኒያውያን ስም እንዲካሄድ ስለማንፈቅድ በብሪታኒያ ታሪክ ግዙፍ የተባለውን የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ የዜግነት ግዴታችንን እንወጣለን» ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ቴሌግራፍ ባሰፈረው ጽሑፍ፣ ዩጎቭ በተሰኘ ድረ-ገፅ የተሰበሰበ የህዝብ አስተያየት የዶናልድ ትራምፕን ጉብኝት የሚደግፉ ዜጎች ቁጥር ከሚቃወሙት የበለጠ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ከተሰበሰበው የህዝብ ድምፅ መካከል 49 በመቶ የሚሆኑት የፕሬዚዳንቱን ጉብኝት የሚደግፉ ሲሆን፤ 36 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ጉብኝቱን እንደማይቀበሉት ገልጸዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱን ጉብኝት ከተቃወሙት ዜጎች መካከል የሴቶች ቁጥር ከወንዶች የላቀ ስለመሆኑም አስተያየቱ አመልክቷል፡፡

ነገር ግን 50 በመቶ የሚሆኑ ወጣት ብሪታኒያውያን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስደተኞችን በተመለከተ ያሳለፉት ውሳኔ ተገቢ አይደለም ብለው እንደሚያምኑና 29 በመቶ የሚሆኑት ግን የፕሬዚዳንቱ መመሪያ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን እንደሚያምኑ አስተያየታቸውን ሰብስቧል፡፡ ካለፈው ዕሁድ ጀምሮ እስከ ረቡዕ ድረስ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ብሪታኒያን እንዳይጎበኙ ፊርማ አሰባስበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ትሬዛ ሜይ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በብሪታኒያ ሊያደርጉት ባቀዱት ጉብኝት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው የድጋፍ ፊርማ የሚያሰባስቡ ወገኖችን ኮንነዋል፡፡

የአገሪቱ ፓርላማ በጉዳዩ ላይ ለመወያየት እ..አ ለየካቲት 20 ቀን 2017 ቀጠሮ የያዘ ሲሆን፤ በዚያኑ ዕለት ታዋቂ ሰዎች የሚሳተፉበትና የሰልፉ አስተባባሪዎች «በብሪታኒያ ታሪክ ግዙፍ የተባለውን የተቃውሞ ሰልፍ እናካሂዳለን» ብለው ቀጠሮ የያዙለት ሰልፍም ይካሄዳል፡፡

 

አንተነህ ቸሬ

 

 

Published in ዓለም አቀፍ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።