Items filtered by date: Saturday, 04 February 2017

 

 

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራንፕ ውሳኔዎችና የህዝብ ተቃውሞዎች፤

 

«ዴሞክራሲ የት ይገኛልቢባል አንደኛ ተጠሪ አሜሪካ ናት። ታዲያ ዛሬ በዚህች «ዴሞክራት» በተባለች አገር ዜጎች ወደኋላ መለስ ብለው ሲያስቡ «ምነ ሆነን ጋሽ ትራምፕን መረጥናቸውያሉ ይመስላል፤ ከአንድ ሳምንት በፊት በምረጡኝ ዘመቻቸውና ባልተጠበቀ የምርጫ ድላቸው የዓለም መነጋገሪያ ሆነው የሰነበቱት ሰው ዶናልድ ትራምፕ፣ አሁን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነዋልና። «አሁን ስልጣን የህዝብ የሚሆንበት ቀን ነው» ሲሉም ጠንካራ ንግግር አሰምተው የነጩን ቤተመንግስት እንቁላላማ ቢሮ ተረክበዋል።

ስልጣን ሲይዙ ምን ይፈጠር ይሆን ሲባልላቸው የነበሩት እኚህ ሰው ሳይውል ሳያድር ከአሜሪካ አልፎ ዓለምን የሚያተራምሱ ውሳኔዎችን ማስተላለፍ ጀምረዋል፤ ቀጥለዋልም። ለምሳሌ ገና በአንድ ሳምንት ትራንስ ፓሲፊክና የሰሜን አሜሪካ ሀገሮች የጋራ ንግድ ገበያን ሰረዙ፤ ውርጃን የሚያግድ ህግ አወጡ፤ የአሜሪካንን የቆዩ የረድኤት ፕሮግራሞችን ለማገድ ተነሱ፤ በእስራኤል የአሜሪካ ኤምባሲን ወደ ኢየሩሳሌም አዛውራለሁ አሉ፤ የኦባማ ኬር ጤና ፕሮግራምን የሚሰርዝ እቅዳቸውን ይፋ አደረጉ፤ በሜክሲኮ ድንበር ላይ ግንብ እገነባለሁ ለዚህም የሜክሲኮ ሰዎች ይክፈሉ አሉ፤ በዚህ አላበቃም፤ አሜሪካ ከሰባት የሙስሊም ሀገራት ስደተኞችን እንዳትቀበል የሚያደርግ ድንጋጌ አወጡ።

ይህ ሁሉ እና ሌሎች የትራምፕ ውሳኔዎች ከአሜሪካ አልፈው መላውን ዓለም የናጡ ጉዳዮች ነበሩ የሚለው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስን የጠቀሰው የ ፐንች ዘገባ ነው። ሰውየው የአንድ ሳምንት የኋይት ሀውስ ቆይታቸው አሜሪካ ከዓለም ነባር ስርዓትና ልማድ ጋር ስትጓዝበት የነበረውን መሰረት ለማናጋት አላነሳቸውም። እኚህ ሰው ከፊታቸው ቢያንስ አራት የስልጣን ዓመታት ይገኛሉ። «በእነዚህ ዓመታትስ አሜሪካና ዓለማችን በእርሳቸው ውሳኔ ምን ይገጥመዋልየሚለው አስጊ ነው ይላል ዘገባው።

በተለይ የፖለቲካ ተንታኞችን አስተያየት የሚያስነብበው ዘገባው እንደሚለው ከሆነ ዓለማችን በትራምፕ አመራር ዘመን በጎ ነገሮች ይገጥሟታል የሚለው ትንበያ ቀቢጸ ተስፋ ብቻ ነው። በርካታ ተንታኞችም በዚህ ጉዳይ ላይ ጨለምተኛ አስተያየት ሲሰጡ ይሰማሉ። እንደውም በትራምፕ ውሳኔዎች ዓለማችን ሊገጥማት የሚችለውን መናጋት ለመቀበል ራስን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ነው የሚመክሩት። እርሳቸው ግን «የአገር ደኅንነት ሚኒስትር ጆን ኬሊ በጣም ጥቂት ችግሮች በስተቀር ሁሉ ነገር በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው ብለውኛል» ሲሉ በተከታታይ በትዊተር ባስተላልለፏቸው መልዕክቶች ገልጸዋል።

ከሁሉ በላይ አነጋጋሪና አስጊ የሆነው ደግሞ ፊርማቸውን ያኖሩበት የኢሚግሬሺን ማስፈጸመሚያ ትዕዛዝ ነው። ይህም ከኢራቅ፣ ከኢራን፣ ከሶሪያ፣ ከሶማሊያ፣ ከሱዳን፣ ከሊቢያ እና ከየመን የሚወጡ ሰዎች ወደአገሪቱ እንዳይገቡ የሶስት ወር እግድ የተጣለበት ትዕዛዝ ነው። የዚህ ትዕዛዝ አፈጻጸም ታዲያ በተለይ በዩናይትድ ስቴትስ አውሮፕላን ጣቢያዎች በፈጠረው መደነጋገር ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ (ግሪን ካርድ) ያላቸው አንዳንድ መንገደኞች ጭምር ለተጨማሪ ጥያቄ እንዲወሰዱ ሆኗል።

በፕሬዚዳንቱ የዕገዳ ትዕዛዝ ዓላማ ከተደረጉት ሀገሮች የተነሱ አንዳንድ መንገደኞች ወደ አሜሪካ በሚመጡ በረራዎች እንዳይሳፈሩ የተከለከሉም አሉ። በዚህ እገዳ ታዲያ ወደ ዘጠና ሺ የሚጠጉ ሰዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጎጂ ይሆናሉ። እኚህ መልዕክታቸውን በትዊተር ማስተላለፍ የለመዱ ፕሬዚዳንት አሁንም በገጻቸው «ከሶስት መቶ ሃያ አምስት ሺ ሰዎች መካከል አንድ መቶ ዘጠኝ ብቻ ናቸው ለጥያቄ እንዲቆዩ የተደረጉት» የሚል ጽሑፍ አሰፈሩ።

«ልብ በሉ...» አሉ «ልብ በሉ፤ አሁን የምንነጋገረው ስለተለያዩ አንድ መቶ ዘጠኝ ሰዎች ነው። በጥቂት ቀናት ሶስት መቶ ሃያ አምስት ሺ የሚጠጉ ሰዎች ከሌሎች አገራት መጥተዋል። ከእነዚህ መካከል አንድ መቶ ዘጠኙ ብቻ ለተጨማሪ ምርመራ ዘግይተዋል።»

የነጩ ቤተ መንግስት የሚዲያ ዘርፍ ጸሐፊ ሾን ስፓይሰር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ «ፕሬዚዳንት ትራምፕ እና ረዳቶቹ የስደተኞች እገዳውን ተጽእኖ አሳንሶ ለማሳየት በብዙ እና በትንሽ ቁጥር መካከል ልዩነትን ማመላከት ይወዳሉ» አሉ። እነዚህ ቁጥሮች ልዩነታቸው ሰፊ የሚመስል የሚሸውዱ ናቸው፤ እንደሂሳብ ግን ልዩነቱን እንየው የሚል መልዕክት አስተላለፉ።

ይህን ሁሉ ተከትሎ ታዲያ ከአንድ ሺ በላይ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካ ሹመኛ ያልሆኑ ሠራተኞች ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያሳለፉትን የስደተኞች እገዳ የሚቃወም ሰነድ ፈረሙ። የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ከምንጮቹ እንዳረጋገጠው የተቃውሞ ሰነዱ አንድ ሺ በሚጠጉ ሠራተኞች የተፈረመና ከዚህ በፊት «ታይቶ የማይታወቅ» የተባለለት ነው። ባለፈው ዓመት እንኳን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሶሪያ የሚከተሉትን ፖሊሲ በመቃወም ወደ ሃምሳ የሚጠጉ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶች ድምፃቸውን ማሰማታቸውን በሶሪያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሮበርት ፎርድ አስታውሰዋል።

በኦባማ አስተዳደር የአውሮፓና አውሮ-ኤዥያ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላውራ ኬኔዲ በትራምፕ አስተዳደር ላይ የወጣውን የተቃውሞ ሰነድ አስመልክቶ ሲናገሩ፤ ሰነዱ በዚህ ፖሊሲ ዙሪያ የውጭ ጉዳይ ሠራተኞች ስጋት ያካተተ እንደሆነ ጠቁመዋል። በተለይ የሕጉ ዝርዝር አፈጻጸም ላይ አጠቃላይና ዝርዝር ትእዛዞች አለመካተታቸውን ዲፕሎማቶችም አልተስማሙባቸውም። «በዓይነቱ የተለየ ዘመን ላይ ነው ያለነው።» ብለዋል የቀድሞ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር።

ሰነዱ «የተቃውሞ ፍኖት» በሚል የተጠራ ሲሆን፤ የትራምፕ አስተዳዳር ያወጣው ፕሬዚዳንታዊ ትእዛዝ «ሊያሳካ ያሰበውን ግብ የማይመታና እንዲያውም በአንጻሩ አሉታዊ የሆኑ ተጽኖዎችን የሚያሳድር ነው» ይላል። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ግን በሰነዱ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል። በተለይ ሰነዱን የፈረሙ ሰዎችን ቁጥርና በመሥሪያ ቤቱ ያላቸውን ስልጣን አልገለጸም።

የነጩ ቤተመንግሥት ቃል አቀባይ ሾን ስፓይሰር፤ የፕሬዚዳንት ትራምፕን የስደተኞች ትእዛዝ የሚቃወሙ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች «ወይ ሥራውን ማስፈጸም፤ አሻፈረኝ ካሉ መልቀቅ ይችላሉ» ብለዋል። አያይዘውም፥ «ይሄ የአሜሪካ ደህንነትን ይመለከታል» አሉ።

 

ሀብታሙ ስጦታው

Published in ዓለም አቀፍ

ግብፅና ካሜሩን የሚያደርጉት የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ይጠበቃል፤

 

በጋቦን አስተናጋጅነት ከጥር ስድስት ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ሰላሳ አንደኛው አፍሪካ ዋንጫ ሊፈፀም አንድ የዋንጫና አንድ የደረጃ ጨዋታዎች ቀርተውታል። ከቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት መብት ጋር በተያያዘ በርካታ አፍሪካውያን ያልተከታተሉት የዘንድሮው አፍሪካ ዋንጫ እንደ ወትሮች ደማቅ ባይሆንም ያልተጠበቁ ክስተቶችን ሲያስተናግድ ሰንብቷል።

ያለፈው አፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮና ኮትዲቯር እስከ ፍፃሜ ትጋዛለች ተብሎ ሲጠበቅ በጊዜ ከውድድሩ መሰናበቷ፤ አልጄሪያ በሪያድ ማህሬዝ፤ ኢስላም ስሊማኒና ያሲን ብራሂሚን የመሳሰሉ ኮከቦች ይዛ ዋንጫውን ለማንሳት ቅድሚያ የተሰጣት አገር ብትሆንም እንደ ሻምፒዮኗ ኮትዲቯር በጊዜ መሰናበቷ ያልተጠበቀ ነበር። የውድድሩ ደጋሽ ጋቦንም ብትሆን ኦባሚያንግን የመሰለ ኮከብ ይዛ ከምድቧ ሳታልፍ መቅረቷ ያልተጠበቀና ለስቴድየሞች የተመልካች ድርቅ መመታት እንደምክንያት መቀመጥ የሚችል ነው።

ባለፉት ሁለት ቀናት በተካሄዱት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች የዋንጫው ተፋላሚዎች ግብፅና ካሜሩን መሆናቸው ተረጋግጧል። ፈርኦኖቹ ቡርኪናፋሶን በመለያ ምት በመርታት የፍፃሜው ተፋላሚ ሲሆኑ የማይበገሩት አንበሶች የጋናን ጥቁር ከዋክብት ባልተጠበቀ የሁለት ለዜሮ ውጤት በመርታት በነገው ፍፃሜ ላይ መቅረብ ችለዋል።

ፈርኦኖቹ የአፍሪካ ዋንጫን ሰባት ጊዜ በማንሳት የሚስተካከላቸው አገር የለም። ይሁን እንጂ ከሰባት ዓመታት በላይ በአገሪቱ በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ተካፋይ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ፈርኦኖቹ ዘንድሮ ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ቢመለሱም ለፍፃሜ ይደርሳሉ ብሎ የገመተ አልነበረም። ይሁን እንጂ አገሪቱ ለተወሰኑ ዓመታት እግር ኳሷ ቢቀዘቅዝም ወዲያውኑ ማንሰራራት የሚችል መሰረት እንዳለው የፍፃሜ ተፋላሚ በመሆን አስመስክረዋል። የማይበገሩት አንበሶችም ቢሆኑ ለበርካታ ጊዜ የፍፃሜ ተፋላሚ መሆን የቻለችውን ጋናን ጥለው ፍፃሜ መድረሳቸውን ብዙዎች አልገመቱም ነበር።

በነገው የፍፃሜ ጨዋታ የሁለቱን አገራት ታሪክ መለስ ብለን ከቃኘነው ተፎካካሪነታቸው ትልቅ ደረጃ የሚሰጠው መሆኑን እናረጋግጣለን። ፈርኦኖቹ የአፍሪካ ዋንጫን ሰባት ጊዜ በማንሳት ቀዳሚ ቢሆኑም የማይበገሩት አንበሶች አራት ጊዜ ሻምፒዮን በመሆን ትልቅ ታሪክ አላቸው። የነገውም ፍፃሜ ፈርኦኖቹ ክብረወሰናቸውን ከፍ ለማድረግ የማይበገሩት አንበሶች ደግሞ ከፈርኦኖቹ ጋር ያላቸውን ልዩነት የሚያጠቡበት እንደመሆኑ ከፍተኛ ፉክክር ይጠበቃል።

ፈርኦኖቹ ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ ቀርበው ሽንፈት የገጠማቸው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ይህም እኤአ በ1962 ኢትዮጵያ ባስተናገደችውና ባነሳችው ሦስተኛው አፍሪካ ዋንጫ አራት ለሁለት ተሸንፈው ዋንጫ ያጡበት አጋጣሚ ነው። ከዚህ ባሻገር ፈርኦኖቹ ሰባት ጊዜ ዋንጫ ሲያነሱ ሁለቱን በፍፃሜ የገጠሙት ከማይበገሩት አንበሶች ጋር ነበር። ፈርኦኖቹ የማይበገሩት አንበሶችን ሁለት ጊዜ በፍፃሜ ጨዋታ ማሸነፍ ሲችሉ አዘጋጅ አገር ነበሩ። ይህም እኤአ 19862006 አፍሪካ ዋንጫዎች ናቸው። አሁን ግን ሁለቱ አገራት ለሦስተኛ ጊዜ በገለልተኛ ሜዳ ለሦስተኛ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ ተገናኝተዋል።

 

ቦጋለ አበበ

 

 

Published in ስፖርት

የሠራተኛው የበጋ ወራት ስፖርት ውድድር በተለያዩ ስፖርቶች እስከ ግንቦት የሚቀጥል ይሆናል፤

 

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) 2009 .ም የበጋ ወራት የቤተሰብ ስፖርት ውድድር ባስተናገዳቸው የሦስት ሳምንት ግጥሚያዎች ጠንካራና ደማቅ ፉክክሮችን እያስተናገደ ይገኛል። በሠራተኛው መካከል የሚካሄደው ውድድር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠንካራ ፉክክሮችን በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ሲያስተናግድ ይስተዋላል። እስከ ግንቦት መጨረሻ በሚዘልቀው የዘንድሮው የበጋ ወራት ውድድርም ገና ከጅምሩ ውድድሮች በጠንካራ ፉክክር እየታጀቡ ነው። ባለፈው ሳምንት በአንደኛ ዲቪዚዮን የእግር ኳስ ፉክክር ቴክኖ ሞባይል ኢትዮጵያ ልማት ባንክን፤ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለ ስልጣን አዲስ ኢንተርናሽናል ኬተሪንግን፤ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ አቢሲኒያ ባንክን በሰፊ የግብ ልዩነት መርታት ችለዋል። በተመሳሳይ በሁለተኛ ዲቪዚዮን ፖል ሬይስና ልጆቹ ኩባንያ ኦርቢስ ኩባንያን በሰፊ የግብ ልዩነት ሲረታ የስ ብራንድና ፉድ ቢቨሬጅ ሄኒከን ቢራዎች አክሲዮን ማህበርን፤ ንፋስ ስልክ ፔፕሲ ኮላ ፋብሪካ ሞኤንኮ ኩባንያን በጠባብ የግብ ልዩነት አሸንፈዋል።

በወንዶች ቮሊቦል የተካሄዱት ሦስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ የሦስት ለዜሮ ውጤት ተጠናቀዋል። ኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ኢትዮጵያ መድን ድርጅትን፤ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ኢትዮጵያ ቆርኪና ጣሳ ፋብሪካን፤ ኢትዮ ቴሌኮም ኢትዮጵያ ግብርና ስራዎችን በተመሳሳይ ውጤት መርታት ችለዋል። በጠረጴዛ ቴኒስ የተካሄዱት አራት ጨዋታዎችም በተመሳሳይ ውጤት ሦስት ለዜሮ መጠናቀቃቸውን የውድድሩ አዘጋጆች ያደረሱን መረጃ ያመለክታል። ኢትዮ ቴሌኮም አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽን፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት መከላከያ ኮንስትራክሽንን፤ ጂኦ ሴንቴቲክስ ኢንደስትሪያል ሄኒከን ቢራዎችን፤ ኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ብራና ማተሚያ ድርጅትን ያሸነፉ ተጋጣሚዎች ናቸው። በቼስ በተካሄዱት ውድድሮች ኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ሄኒከን ቢራዎችን፤ ኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ፋፋ ምግብ አክሲዮን ማህበርን ሁለት ለዜሮ በሆነ ተመሳሳይ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል። በዳማ ውድድር ጂኦ ሴንቴቲክስ ኢንደስትሪያልና ኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ተጋጣሚዎቻቸውን የረቱ ሲሆን፤ በዳርት ውድድር አንበሳ የከተማ አውቶቡስና ጂኦ ሴንቴቲክስ ኢንደስት ሪያል ድል ቀንቷቸዋል።

ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲውሉ በወንዶች ቮሊቦል አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ኢትዮጵያ ቆርኪና ጣሳ ፋብሪካን ይገጥማል። የስ ብራንድ ፉድና ቢቨሬጅ ኢትዮጵያ ግብርና ስራዎችን የሚገጥም ይሆናል። ሁለቱም ጨዋታዎች በሙገር ሜዳ ከስምንት ሰዓት ጀምሮ ይከናወናሉ። በወንዶች ጠረጴዛ ቴኒስ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን፤ ስብሃቱና ልጆቹ ሃኒከን ቢራዎችን፤ ጂኦ ሴንቴቲክስ ፋፋ ምግብን ይገጠማሉ። በሴቶች በሚደረገው አንድ ጨዋታም ብርሃንና ሰላም ኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትን ያስተናግዳል። ሁሉም ጨዋታዎች ዛሬ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ መወዳደሪያ ላይ ከስምንት ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳሉ። በወንዶች የቼስ ውድድር ብርሃንና ሰላም ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት፤ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ ኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ዛሬ በተመሳሳይ ሰዓትና ሜዳ የሚጫወቱ ይሆናል። በዳማ ውድድር ብርሃንና ሰላም ጂኦ ሴንቴቲክስን፤ ኢትዮጵያ ፖስታ አንበሳ የከተማ አውቶቡስን የሚገጥሙ ሲሆን በተመሳሳይ ሰዓትና ቦታ በዳርት፤ ገበጣና ከረንቦላ ጨዋታዎች ውድድሮች እንደሚካሄዱ ታውቋል።

በእግር ኳስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት፤ መከላከያ ኮንስትራክሽን ከቴክኖ ሞባይል ነገ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ በሙገር ሜዳ ይገናኛሉ። ኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከኢትዮ ቴሌኮም፤ ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ካምፓኒ ከኦርቢስ ኩባንያ ነገ ከሰዓት በኋላ በመድን ሜዳ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ከቃሊቲ ብረታብረት፤ ሞኤንኮ ኩባንያ ከአለማየሁ ንጉሴ ፒፒ ከረጢት ማምረቻ ነገ ጠዋት በስብስቴ ሜዳ የሚያደርጉት የእግር ኳስ ውድድርም የሚጠበቅ ነው።

 

ቦጋለ አበበ

Published in ስፖርት

የዓለማቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አበረታች መድሃኒት ተጠቃሚነት ላይ ጠንካራ አቋም ይዞ መንቀሳቀስ ከጀመረ ሰንብቷል። በ2008 የቤጂንግና 2012 ለንደን ኦሊምፒክ በተሳተፉ አንድ ሺ አትሌቶች ላይ መለስ ብሎ ባደረገው የደም ናሙና ምርመራ የተለያዩ ቅሌቶች ይፋ እየሆኑ ነው። ከእነዚህ መካከል በለንደን ኦሊምፒክ በሴቶች የሦስት ሺ ሜትር መሰናክል ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችው ሩሲያዊታ አትሌት ዮሊያ ዛራፖቫ ስትሪዮድ ትሪናቦል የተባለ የተከለከለ ንጥረ ነገር ተጠቅማ ስለተገኘች የአትሌቷ ውጤት በመሰረዙ ምክንያት የውጤት ሽግሽግ (ማሻሻያ) መደረጉ ይታወሳል፡፡በውጤቱ ለውጥ ሳቢያ ቱኒዛዊቷ አትሌት ሀቢባ ጋራቢ የወርቅ፣ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሶፍያ አሠፋ የብር፣ እና ኬንያዊቷ አትሌት ሚልካ ቼሞዝ የነሐስ ሜዳሊያዎችን እንዲያገኙ ተወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በተስተካከለው አዲስ የውጤት ማሻሻያ መሰረት ከትናንት በስቲያ በዲሪምላይነር ሆቴል የአለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል የሆኑት ወይዘሮ ዳግማዊት ግርማይ፣ የተለያዩ የስፖርት አመራሮች፣ የኮሚቴው ሥራ አስፈጻሚ አባላት ፣የመገናኛ ብዙሃን አካላት እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ለአትሌት ሶፍያ አሠፋ የሜዳሊያ ሽልማት ሥነ-ስርዓት አድርጓል።

አትሌት ሶፊያ አሰፋ የብር ሜዳሊያዋን የአለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል በሆኑት ወይዘሮ ዳግማዊት ግርማይ ተጠልቆላታል። ሶፊያ ከስነ ስርዓቱ በኋላ ከጋዜጠኞች በቀረበላት ጥያቄ « አራት ዓመት ቆይቶ ጊዜውን ጠብቆ መቷል፤ እቺ ቀን የውድድሩ እለት ብትሆን ደስታዬ እጥፍ ድርብ በሆነ ነበር፤ የላቤ ዋጋ ዘግይቶም ቢሆን በመምጣቱ ደስተኛ ነኝ» በማለት አስተያየት ሰጥታለች። ለአገር ክብርም ቢሆን ይህ ውጤት በወቅቱ ቢሆን ኖሮ የበለጠ ደስታን እንደሚፈጥር የገለፀችው ሶፊያ በጥቅማ ጥቅም ረገድ ይህ ውጤት በወቅቱ ቢሆን ኖሮ የበለጠ ተጠቃሚ እንደምትሆን ገልፃለች። ሜዳሊያው ወደ ኢትዮጵያ በመመለሱ እንደተደሰተች የገለፀችው ሶፊያ፤ ዝግጅት ተደርጎ የሽልማት ስነ ስርዓቱ በመከናወኑ ምስጋናዋን አቅርባለች። አበረታች መድሃኒት ተጠቅሞ ማሸነፍ ትርጉም እንደሌለው የምታብራራው ሶፊያ «አንድና ሁለት ሰው ሳይሆን የዓለም ህዝብን እንደማጭበርበር ይቆጠራል» ትላለች። በአበረታች መድሃኒት የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፎ ከጊዜ በኋላ ሲደረስበት መመለስ ሜዳሊያ ብቻም ሳይሆን ሁሉን ነገር ያሳጣል ስትልም ለሌሎች አትሌቶች ምክሯን ለግሳለች። በቀጣይ ክረምት በለንደን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመሳተፍ ጠንክራ እየሰራች እንደምትገኝ ያስረዳችው ሶፊያ ሽልማቱ የበለጠ ለመስራት እንደሚያነሳሳት ተናግራለች።

ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪኳ ከሞስኮ 1972 ኦሊምፒክ ከ32 ዓመታት በኋላ በመሠናክል ውድድር የአትሌት እሸቱ ቱራን ገድል የደገመችው አትሌት ሶፍያ ናት። በርቀቱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በሴቶች ሜዳሊያ በማጥለቅ የመጀመሪያ የሆነችው አትሌት ሶፍያ አሠፋ በለንደን ኦሊምፒክ ውድድሩን የፈፀመችበት ሰዓት 9 ደቂቃ ከ 06.72 ሴኮንዶች ነበር፡፡ ሶፊያ አሁን የውጤት ሽግሽግ ሲደረግ ግን የብር ሜዳሊያ በርቀቱ በማስመዝገብ በታሪክ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሆናለች። በለንደን ኦሊምፒክ የሶፊያ ብቻም ሳይሆን አብረዋት የተወዳደሩ ሁለት ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ውጤት ተሻሽሏል። አምስተኛ ሆና ያጠናቀቀችው አትሌት ህይወት አያሌው የዲፕሎማ ባለቤት ስትሆን ሌላኛዋ አትሌት እቴነሽ ዲሮ ከስድስተኛ ወደ አምስተኛ ደረጃ ውጤቷ ተሻሽሏል። ሶፊያ ከለንደን ኦሊምፒክ በተጨማሪ በ2011 የዴጉ ዓለም ሻምፒዮና ስድስተኛ ሆና ያጠናቀቀችበት ውጤት ወደ አምስተኛ ተሸጋሽጓል።

አትሌቷ በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች፣ በአፍሪካ እና በአለም ሻምፒዮናዎች ላይ በመሳተፍ ለሀገሯ አኩሪ ድሎችን አስመዝግባለች፡፡ ለአብነት ያህል ባለፈው አመት በኮንጎ ብራዛቪል ላይ በተካሄደው የ3000 መሰናክል ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ እና በ2013 በሞስኮ በተካሄደው የአለም ሻምፒዮና ላይ የነሐስ ሚዳሊያ ማስመዝገቧ ይታወሳል፡፡

የተከለከለ አበረታች ንጥረ ነገር በሽንት ምርመራ የተገኘባት ሩሲያዊቷ አትሌት ዮሊያ ዛራፖቫ ከአትሌቲክስ ስፖርት ከመታገዷ በተጨማሪ እ..አ ከ ሐምሌ 2011 እስከ ሐምሌ 2013 ያገኘቻቸው ክብሮች፣ ሜዳሊያዎች እና ጥቅሞች ሙሉ ለሙሉ ተሰርዘውባታል፡፡

ኢትዮጵያ በለንደኑ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች በአትሌቲክስ ስፖርት ከ400 ሜትር እስከ ማራቶን ድረስና በውሃ ዋና ስፖርቶች በመሳተፍ በድምሩ ባገኘችው 7 ሜዳሊያዎች ከዓለም 24ኛ ከአፍሪካ 2ኛ በመውጣት ማጠናቀቋ ይታወሳል። የተስተካከለው ውጤት ታርሞ ሀገራችን እስካሁን በተሳተፈችባ ቸው 13 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች 22 የወርቅ፣ 10 የብር፣ እና 21 የነሐስ በድምሩ 53 ሰብስባለች፡፡

 

ቦጋለ አበበ

 

 

 

Published in ስፖርት
Saturday, 04 February 2017 19:01

ሐረርን በምሽት

ብዙ የምታደንቁትን፤ ብዙም የምትሰሙለትን ነገር በዓይን ማየትን የመሰለ ነገር ለካ የለም! እጅግ ጠቢብ የሆነ ሰው ስለአንድ ነገር ቢናገር፤ ያንንም ደግሞ ምስል ከሳች አድርጎ በሚማርክ መንገድ ቢገልጠው፤ በዛ ምንኛ ብትደነቁና የልብ አድርስ፣ የልብ አውቃ ብትሉት። መቅረጸ ምስሉ ምን ያህል የረቀቀ ቢሆን፤ የራቀውን አቅርቦና አጉልቶ ቢያሳይ እመኑኝ! በፍጹ እምነት ካልሆነ በቀር እንደራስ ምልከታ እንደራስ ምስክርነት አይሆንም።

ከዚህ በፊት እንደው በስም ብቻ እወዳት፤ በትዕይንተ መስኮት ብቻ አያት፤ በወሬ ብቻ አውቃት፤ በንባብም ብቻ እገልጻት የነበረችውን ሐረር ለማየት እድሉን አገኘሁ። ይህቺ የምወዳት ከተማ ታዲያ ህዳር 29 ድግስ እንደነበረባት ታስታውሳላችሁ። ከዛ መልስ ዙሪያዋን ለማስጌጥ የተሰቀሉትና ያልተነሱት የሸራ ላይ ጽሑፎች ለምስክርነት የቀሩ ይመስላል።

በነገራችን ላይ በከተማዋ የቆየሁት ለ14 ሰዓታት ብቻ ነው። ያውም ደግሞ ከምሽት አስራ ሁለት ሰዓት ጀምሮ በማግሰቱ እስከ ማለዳው ሁለት ሰዓት ድረስ ያለውን ልዩነት መቁጠር ነው። ይህ የሆነው ጥር ወር የጥምቀት በዓልን አንድ ቀን ወደፊት አልፎ በ13 በቀዳሚት ሰንበት ነው። ይህም አስራ ስድስተኛውን የአርሶ አደሮች ቀን በሶማሌ ክልል ጂግጂጋ ከተማ ለማክበር ወደዛ በሚደረግ ጉዞ መካከል ማረፊያችን ሐረር በመሆኗ ነው።

ታዲያ ምሽት ላይ ከጉዞው ጥቂት እረፍትና ከቀኑ ውሎ መዝጊያ ምግብ በኋላ የሥራ ባልደረቦች ሰብሰብ ብለን ከተማዋን በምሽት በጥቂቱ ለመቃኘት በእግራችን የተወሰነ መንገድ ለመሄድ ወጣን፤ ወይም «ወክ» ለማድረግ። እንግዲህ ይህን ስነግራችሁ ከጉዞ የተመለሰና የደከመው ሰው፣ ነፋሻማ በሆነና ትንሽ ቅዝቃዜ ባለው አየር ምን ያህል «ወክ» ያደርጋል ብላችሁ አስቡ፦ ቀጥሎ የማወጋችሁና እስከአሁንም ያልኳችሁ ሁሉ የተቀዳው ከዚህ እጅግ በጣም ደቃቅ፣ ውስን ቆይታ ላይ ነው። ቢሆንም ሐረርን ሳላያት እንዲሁ አይደለ የወደድኳት? የሰላሳና የአርባ ደቂቃ የእግር መንገድ በዙሪያዋ ማድረግ ምን ያህል ይገዝፍ።

ርዕሱን «ሐረርን በምሽት» የማለቴ ምክንያት እንግዲህ እንኳን ሰው ጅብም ከሰው ተላምዶ የሚኖርባት ከተማ ስለመሆኗ ላጠይቅ አለመሆኑን አውቃችሁልኛል። ከሐረር ሰዎች ጋር የሚወደሰውን ጨዋታቸውን ለመካፈል በሚያበቃ ደረጃ አልተዋወቅሁም፤ «አቦ»አቸውን መስማት በሚያስችል መጠን አብሬያቸው አልቆየሁም፤ ጣጣ የሌላቸው የፍቅር ሰዎች መሆናቸውን አየሁ እል ዘንድ ደቂቃ እንኳን አብሬአቸው አላሳለፍኩም። እንዲያ እንደሆኑ ግን በብዙ ምስክሮች በፍጹም እምነትም አውቃለሁ።

በዛ ምሽት የጀጎልን ግንብ አልፈን የአስፋልቱን ቁልቁለትና ዳገት በዝግታ እርምጃ ስንሄድበት የታዘብኩትን ያየሁትን ነገር ላጋራችሁ ብቻ ግን ተችሎኛል። እንደው ነገሬ ሁሉ «ሐረርን አየኋት» ብሎ እንደ ልጅ እንቁልልጭ እንደማለት መሰለብኝ ይሆን? አልሰሜን ግባ በለው አትሉኝ!

ሐረር እንደስሟ በሚገባ ያላደገች እንደሆነች የሚናገሩ ሰዎችን እሰማለሁ። ከቁሳዊ ሀብቷ ይልቅ ሰዋዊው ሀብት በልጦ የሚታይባት፤ በዚህም የምታስቀና መሆኗን ግን ማንም የሚክደው አይሆንም። የስነ ምጣኔ ተንታኙ፣ የከተማና የመሰረተ ልማት ዘጋቢው፣ የልማቱ ሰራዊትና መሰሎቻቸው ሁሉ ስለከተማዋ የየራሳቸው ትንታኔ ይኖራቸዋል። ሐረር በእድገት ላይ ያለች አገር አንድ ክፍል ናትና የሚጠበቁና የሚታወቁ ክፍተቶች አሉ። ብቻ ነገሩን ሁሉም ታዝቦት ይሁን አላውቅም፣ ከዚህ በፊት ተብሎም ከሆነ አላስታውስም ግን አንድ ነገር ቀጥሎ እነግራችኋለሁ።

እንዳልኩት በእርጋታ እርምጃ የተንቀሳቀስነው እጅግ ውስን ደቂቃ ነው። በዛ መካከል አስፋልት የሆነና መጪና ሂያጁን የሚያስተናግድ በሁለት አቅጣጫ የተዘረጋን መንገድ ከመካከለቸው አድርገው ፊት ለፊት ለውይይት የተቀመጡ የሚመስሉ ህንጻዎች ይታያሉ። ህንጻ አንዱ የከተሞች ሥራ ይሆናል እንጂ የእድገት ምልክት እንዳልሆነ በእርግጥ ይታወቃል። እነዚህ ህንጻዎች ግን ለየት ይላሉ። እንዴት በሉ፤ ብትፈልጉ ፓሪስ፣ ቢያሻችሁ ኢንግሊዝ፣ አይ ካላችሁ አሜሪካ፣ ከተስማማችሁ ቻይና ወስዳችሁ ብታቆሟቸው ያለጥርጥር ያያቸው ሰው ያውቃቸዋል፤ የሐረር ከተማ ህንጻዎች ናቸው ይላል። ያንን የሚለው ሰው የተለየ አስማት ኖሮት አይደለም፤ ህንጻዎቹ ማንነት ስለተቀባባቸው ያስታውቃሉና ነው።

ልብ ብላችሁ ከሆነ በአብዛኛው በተለይ በዋና ከተማይቱ አዲስ አበባ ያሉ ቤቶች ኢትዮጵያዊ አይደሉም ወይም ቤቱ ውስጥ ካልገባችሁ በቀር በዛ ቤት ውስጥ ማን ሊኖር ይችላል የሚለውን መገመት የማይቻል ነው። መቼም አዲስ አበባ ዘመነኛ የሆነውን «ስልጣኔ» በመቀበል ቀዳሚ በመሆኗ ዱላው ፈጥኖ ያርፍባታል እንጂ የበርካታ ከተሞቻችን ቤቶች እውነት ይሄ ነው። ደግሞስ መኖሪያ ቤት ችግር ሆኖ በሚነሳባት አገር ስለግንባታው ማንሳት ምን ይሉታል? ትሉ ይሆናል። ግን ወደፊት በሚመጣ አንድ ቀን ይህ ጉዳይ የሚነሳ ይመስለኛል።

አውሮፓውያን ከየትም አገር ሲመጡ ራሳቸውን የሚያዩ አይመስላችሁም? እኔማ ልክ የአንዱን «ሪል ስቴት» የቤት ግንበታ ሲያዩ እንደው ከስሙ ጀምሮ ይደነቁና «ይህቺ እንግዳ ተቀባይ አገር ቤታችንን የሚመስል ቤት ሠርታልን የለም እንዴየሚሉ ሁሉ ይመስለኛል። ግንባታው አያምርም አይደለም፤ ያም ጥበብ ነውና። ነገር ግን የእኛ ሳይሆን የእነርሱ ማንነት በቤታችን ላይ ጎልቶና ደምቆ ተስሏል፤ ተስሎም ይታያል።

በእኔ እምነት ሐረር ለሁሉም ምሳሌ የምትሆን ከተማ ናት። የሚገርማችሁ በተለይ ከሐረሪ ክልል መግቢያ ጀምሮ ግንባራቸው የጃጉልን ዓይነት ቅርጽ የያዘ ቤቶችን ታያላችሁ። አልያም ዝቅ ስትሉ አጥራቸው እንዲያ ነው፣ ሐረርን ተቀብተዋል፣ ማንነትን የሚናገሩ ተደርገዋል። ይህ ስለውጪ ጎብኚ ተብሎ የተደረገ አይደለም፤ መስህብም ለመሆን አይደለ። ነገር ግን ማንነትን ስለማቆየት ነው።

ታዲያ ዋና ከተማችንም የሁሉ መናኽሪያ ትንሿ ኢትዮጵያ የምትባል ናትና ከመባል በዘለለ መሆንን ብትላበስ፤ የእኔ ያሏትን ማንነትን ብትቀባ፤ ከዓይን የራቀ ነውና ለዓይን የሚሆነውን የራስን ነገር ብታቀርብ በእውነት ከልቤ ተመኘሁ። ለምንም ነገር በእርግጥ አይረፍድም ደግሞም ትውልድ ቀጣይ ነውና ዛሬም ባይሆን ነገ መሆኑ አይቀሬ ነው። እንደው የላሊበላን የህንጻ ጥበብ፤ የሐረርን ኪነ ህንጻ ቅመም፤ ብቻ አገርኛ አገርኛ የሚሸት ህንጻ ከተማዎች ቢኖራቸው እንዴት ባማረብን! ከሐረር በተወሰኑ ደቂቃዎች ይህን ማየት ከተቻለ የከረምን እንደሆነማ ስንት ነገር ይገኝ ነበር! ሐረርን ማለዳ ተሰናብተን ወደ ጅግጅጋ ስንሄድ ሳለን ይህን ሳስብ ነበር።

 

ሊድያ ተስፋዬ

 

 

Published in መዝናኛ
Saturday, 04 February 2017 18:57

ክብር- ለአርብታ አደሯ

 

ምሳሌ የሚሆኑ አርብተው አደሮች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማት ሲቀበሉ፤

 

የሰው ልጅ በተፈጥሮ በታደላቸው ጸጋዎች ይገለገል ዘንድ እንዲረዳው ስርዓትን አበጀ፤ ደግሞም በወንድና በሴት መካከል ሥራዎችን ተከፋፈለ። አለመቻል የክፍፍሉ ምክንያት አልነበረም፤ አለመቻልን ይዞ የሚወለድ የለምና፤ ነገር ግን አንዱ ላይ ሁሉም ጫና እንዳይበዛ ሲባል ነው። ይህ ግን በጊዜ ሂደት ማኅበረሰቡ አንዱን ከፍ ሌላውን ዝቅ ከማድረግ አልከለከለውም።

አጣምመው እንደተከሉት ዛፍ በማኅበረሰቡ ውስጥ እንደተንጋደደ ከቆየ አስተሳሰብ መካከልም ይህ አንዱ ነው። «ሴት የማትችለው አለ» ብሎ ማሰብ። ይህ ነው ዛሬ ላይ ስለእኩልነት እንድናወራ፣ ልዩ ድጋፍ ለሴቶች ብለን እንድንነጋገር ያስገደደን። በነገራችን ላይ በ«ሴት አትችልም» ውስጥ «የሰው ልጅ የማይችለው ነገር አለ» ብሎ ማሰብ እንዳለ ልብ ይሏል።

«እኛ ጋር እንዲህ ብሎ ነገር የለም፤ እንደውም አብዛኛው ኃላፊነት የሴቶች ነው»። ይላሉ የአፋር ክልል ተወላጅ የሆኑት ወይዘሮ አናዊታ ኢብራሂም። በባህል ልብስ ደምቀዋል፤ ከልብሳቸው በላይ ደግሞ ፈገግታና እናትነት የተላበሰ መልካቸው ይጎላል። ከአንገታቸው ላይ በአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለም የተሸለመን ገመድ በጠባብ ቀለበቱ ያሾለከ ወርቃማ ሜዳልያ ይታያል። ከግራ ወደቀኝ ያገለደሙት አርበ ጠባብ ባለቀይ ቀለም ጨርቅ ላይ በነጭ የታተመ ጽሑፍ አለ፥ «ታታሪ የልማት ጀግና አርብቶ አደር ተሸላሚ» የሚል።

ከእኚህ ብርቱ ወይዘሮ ጋር የተገናኘነው በሶማሌ ክልል ጂግጂጋ ከተማ ባለፈው ሳምንት ጥር 17 ቀን 2009 .ም በተከበረው የአርብቶ አደሮች ቀን በዓል ላይ ነው። በዓሉ በዚህ ዕለት ሲከበር ለ16ኛ ጊዜ ነው። መሪ ሃሳቡም «የአርብቶ አደሩ የሰላምና የልማት የላቀ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለህዳሴያችን» የሚል ሲሆን እንዳልኳችሁ ወይዘሮ አናዊታ ተምሳሌት ይሆናሉ ተብለው ከተሸለሙ አርብተው አደሮች መካከል ናቸው።

ለዚህ ሽልማት ያበቃቸው ለምግብ ዋስትና ራስን በመቻል እና ያመረቱትን ደግሞ ለገበያ በማቅረባቸው ነው። በተጨማሪም ቤቶች ገንብተው ያከራያሉ፤ አነስተኛ ሱቅ ከፍተውም ይነግዳሉ። እንዲሁ በዓይነ ህሊና ሳሏቸው ብትባሉ የሴት ቁንጮ የሴት አውራ አድርጋችሁ ብትስሏቸው አትሳሳቱም። እኚህ እናት በሚኖሩበት የአፋር ክልል ምንም እንኳን ሴቶችን የሚመለከት ጎጂ ባህልና አመለካከት ቢኖርም ሰብረው ለመውጣት የቻሉ ናቸው። አስቡት! ከተማ ላይ የምትኖር ከሞላ ጎደል ሁሉ የተሟላላት ሴት ለትልቅ ደረጃ ስትደርስ ቆመን እንደምናጨበጭብ ሁሉ በብዙ የአመከለካከት እሾህና ተራራ አቋርጠው ለስኬት የሚበቁ ሴቶችንማ ምንኛ ልናደንቃቸው ይገባ!

ወይዘሮ አናዊታ ከዚህ በፊት ተሸላሚ እንደሆኑ ያስታውሳሉ፤ ይህም ከዓመት ዓመት የበለጠ እንዲያድጉ ለውጥም እንዲያመጡ ረድቷቸዋል። በየዓመቱ የሚያገኙትን ትርፍና ገንዘብ ደግሞ ዝም ብለው ተቀማጭ እንደማያደርጉት ይናገራሉ። ይልቁንም እንዲህ አሉ፤ «ገንዘብ ከማስቀመጥ ይልቅ አዲስ ሥራ ፈጥሬ እዛ ላይ አውለዋለሁ፤ አዳዲስ ቤቶችንም አሠራለሁ።» ወይዘሮ አናዊታ ምንም እንኳን የቤት ውስጥ ኃላፊነቱ እያለ፤ የሰባት ልጆች እናትና ልጆቻቸውን አስተማሪ ቢሆኑም ሥራቸውንም በሚገባ መወጣት ችለዋል። በእርግጥም ለተሸላሚነት የበቁት ያንን በመወጣታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው።

በተመሳሳይ በእለቱ ተሸላሚ ከሆኑ አርብቶ አደሮች መካከል ወይዘሮ ሆደል መሃመድ ኢስማኤል ይገኙበታል። ወይዘሮ ሆደል በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን ሃርሺም ወረዳ ነዋሪ ናቸው። ሴት ሆኖ አርብቶ አደርነት ምን ይመስል ይሆን የሚለው ጥያቄ ለሆደል ቀላል ነበር፤ «እኛ ጋር አዲስ ነገር አይደለም፤ አርብቶ ማደር የለመድነውና ዘመናት አብሮን የኖረ ነው።» ብለዋል።

አርብቶ አደርነት አንዱ የኑሮ ዘይቤ ነውና ለነዋሪው «ከባድ ነው ወይስ ቀላልየሚለው ጥያቄ የተለየ ትርጉም አይሰጥም። በትክክልም በራስ አስተሳሰብና በራስ ወሰን ልክ የተሻለ የሚባለውን ኑሮ መኖር ቀላል አይደለም። በየትኛውም ዘርፍ ከፍ ወዳለ ደረጃ ለመድረስ የፈለገ ብዙ ጥረት ይጠይቀዋል፣ የዕለት ጉርስን ለመሸፈን ብሎም ለነገ ለመትረፍ መትጋትን ይፈልጋል። ሻካራ እጆች አይደሉ የእውነተኛ ታታሪዎች ምልክት?!

ወደቀደመ ነገራችን እንመለስ፤ ሆደል መሃመድ ለዚህ ሽልማት ያበቃቸው ያላቸውን ግመሎችና ከብቶች በስነስርዓት ቀልበው ጥራት እንዲኖራቸው በማድረግና እነዛንም ለገበያ በማቅረብ ነው። በተጨማሪም ገበያው የሚፈልገውን የወተት ምርትም በማቅረብ በኩል ምሳሌ መሆን የሚችሉ በመሆናቸው ነው የተመረጡት።

ሥራቸውን በተመለከተ አያይዘው ሲናገሩ በክልሉ አርብቶ አደር ቢሮ ከከብቶች ብዛት ይልቅ በጥራታቸው ላይ መሥራት ስኬታማ እንደሚያደርጋቸው እንደተረዱ ይናገራሉ። ይህም ሽልማትና ስኬት ወደፊት ራሳቸውንም ሆነ ሌሎች ሴት አርብተው አደሮችን የሚያነሳሳ እና የሚያተጋ እንደሆነ እምነታቸውን ይገልጻሉ። ደግሞም ወይዘሮ ሆደል መሀመድ የልጆች እናት ናቸው፤ ልጆቻቸውን ውጤታማ ለማድረግ መትጋታቸው አልቀረም። «ልጆቻችን ትምህርት ቤት ሲሄዱ እኛ ከብት እንጠብቃለን፤ ሥራችንን እና እንደወላጅ የሚጠበቅብንን፤ ሁለቱንም አጣጥመን እየሄድን ነው» ብለዋል።

እንደ አናዊታ እና ሆደል መሀመድ ያሉ አርብተው አደር እናቶች በተለይ በአራቱ የአርብቶ አደር ክልሎች ማለትም በኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ አፋር እና ደቡብ ክልሎች አሉ። እነዚህ ሰዎች በቀደሙት ጊዜያት ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀሳቸው ምክንያት ዘላን ተብለው ይጠሩ የነበሩና ከዛም በራሳቸው ጥረት የየራሳቸውን የለውጥ ሻማ የለኮሱ ናቸው።

በበዓሉ ማጠናቀቂያ ላይ እነዚህ አርብተው አደር ተወካዮች ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ለውይይት ተቀምጠው ነበር። በዚህ ውይይት ላይ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል አንደኛው የመንገድ ሥራን የተመለከተ ነው። እነዚህ ክልሎች ለወላድ እናቶች የሚውሉ አምቡላንሶች ያሏቸው ቢሆንም በመንገድ ችግር ምክንያት መኪናዎቹ እየተጎዱ ከአገልግሎት መስጫ ውጪ እየሆኑ ነው የሚል መፍትሄ ስጡን ጥያቄ ተነስቷል። ይህም ብቻ ሳይሆን እንደ አርብተው አደርነታቸው ድርቁን ለመከላከል መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ሃሳብ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት ከሞላ ጎደል የጥገና አቅምን ከማሳደግ አንጻር ክልሎች እንዲሠሩና የፌዴራል መንግስትም እገዛ እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት። አያይዘውም «የእናቶችን ችግር ለመቅረፍ የጀመርነውን እንቅስቃሴ እንቀጥላለን» ብለዋል። ወቅት ጠብቆ የሚከሰተውን ድርቅ በተመለከተ ድርቁን ተቋቁሞና አብሮ ለመዝለቅ ውሃን ማዕከል ያደረገ የሥራ እቅድ እንዳለና ያንንም ተግባራዊ ለማድረግ በተለይ በጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ መልካም ጅማሮዎችና ሥራዎች እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በዚህ አጋጣሚ፤ በፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ልማት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አርብቶ አደሩን በተመለከተ ከሚካሄደው ሥራ መካከል አርብቶ አደሩ በተወሰነ መልኩ እርሻን እንዲለማመድ ማድረግ ነው። ይህም ቢያንስ ለእንስሳቱ መኖ ለራሱም ምግብ አልፎም የፍራፍሬ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብን ማስቻል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደተናገሩትም እቅዱ ሁሉ ተፈጻሚ ሆኖ ሥራው ከተጠናቀቀ፤ ውጤቱ የሚሆነው ዘመናዊ የሆነ አርብቶ አደር ነው። ይህ በተግባር በፍጥነት ተዳርሶ ባይታይ እንኳን ተጠያቂነት ይኖር ዘንድ በቃልና በጽሑፍ ሰፍሯልና ይህ መልካም ነው።

እንግዲህ በአራቱ የአርብተው አደሮች ክልል ወንድ ብቻ አይደለ፤ ሴት አርብታ አደርም አለች። ልጅ ከመውለድ ባሻገር፣ ቤት ውስጥ እናትና ሚስት ሆና ከማገልገል በተጨማሪ ትልቅ የሚባሉ የልማት ሥራዎችን መሥራት እንድትችል በብዙ ምስክር ማየት ይቻላል። በእርግጥ በዚህ አምድ ስለአርብቶ አደርነት ስላነሳን እንጂ አርብታ አደሯን ወደኋላ ሊጎትት የሚችል በርካታ ጎጂ ባህል እንዳለ እናውቃለን።

ዛሬ ለዚህ ሽልማት የበቁት ግን በደንገዝጋዛው ላሉት መንገዱን የሚያሳይ ፋኖስ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም። እኛ ምንአልባት እንዲህ ነው፤ እንዲያ ነው ብለን እንናገር ይሆናል፤ አይተናልና። አርብታ አደሯ ግን ታውቃለች፤ ኑሮዋ ያ ነውና። በእርሷም በመሳዮቿ ጥረት ዘመናዊ አርብቶ አደር ሲፈጠር ቀዳሚ ተጠቃሚ እርሷ፤ አርብታ አደሯ የምትሆን አይመስላችሁም? ሰላም!

 

ሊድያ ተስፋዬ

 

Published in ማህበራዊ

ፕሮፌሰር እስቅያስ አሰፋ ይባላሉ፤ ሀላፊነታቸውን በሚመለከት “ሁለት ባርኔጣ አለኝ” ይላሉ፡፡ አንደኛው ፕሮፌሰርነታ ቸው ነው፡፡ ቨርጂኒ ውስጥ ባለ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ፕሮግራም ግጭት አፈታትና የእርቅ ጉዳዮችን በሚመለከት ያስተም ራሉ፡፡ “ሰላምና እርቅ ትርጉምና መንገዶች” የሚል መጽሀፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ ሁለተኛው ባርኔጣቸው አለም አቀፍ የእርቅና የሰላም ጉዳዮች ታዋቂ አደራዳሪ ሆነው በመስራት ከ20 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያዊ ሰው ናቸው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባቀረበላቸው ጥሪ ተጋብዘው በእርቅ እና ሰላም ዙሪያ አለም አቀፍ ልምዳቸውን ሊያካፍሉ እዚህ አዲስ አበባ በተገኙበት ወቅት በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ እንዲህ ለንባብ ቀርቧል፡፡ ዝርዝሩን እነሆ…

አዲስ ዘመን፡- እርቅ ማለት ምን ማለት ነው?

ፕሮፌሰር እስቅያስ፡- ግጭት ተፈጥሮ ሰው ሲጎዳዳ፤ በመጎዳዳቱ ደግሞ ቂም ሲያያዝ፤ ቂሙም በሁለት ወገኖች ብቻ ሳይሆን ወደ ሌላም ወገን ሲዛመት፤ በዚህም ወደ ልጆች ቤተሰቦች፥ እንዲያ እያለ ይሰፋል። በቆየው ባህላችን አንድ አባቱ የተገደለበት ሰው የገዳዩን ፤ ወይም ገዳዩን እንኳ ባያገኘው የገዳዩን ወገን ፈልጎ መግደል እንዳለበት ያምናል።

በዚህ ሁኔታ ያ ቂም አይበርድም ማለት ነው። ይህ ሁኔታ አዙሪት ሆኖ እየተሽከረከረ ጥፋት እያስከተለ ይነጉዳል። ስለዚህ ግጭት ሲኖር በግጭት ምክንያት መጎዳዳት ሲኖር በመጎዳዳት ምክንያት መገዳደል፤ ቂም፣ የነበረው መልካም ዝምድና ሲሻክር ሲበረዝና ሲበላሽ እርቅ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። በመሆኑም እርቅ በዚህ ሂደት የተበላሸውን ግንኙነት ለማደስና የቆየውን በጎ ዝምድና እንደገና ለመመስረት የሚረዳ ሂደት ነው እርቅ። ስለዚህ በተለይ ከባድ ግጭት ካለ በሁሉ አይነት መንገድ መፍትሄ ለማግኘት ከተፈለገ እርቅ ፍቱን ዘላቂ መፍትሄ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የግጭት መንስኤ ናቸው ተብለው የሚነሱት የትኞቹ ናቸው?

ፕሮፌሰር እስቅያስ፡- የግጭት መንስኤዎች በአንድ ብቻ የሚወሰኑ አይደሉም። ሁለተኛ ደግሞ የግጭት መንስኤ የምንላቸው የተቀራረበ እና የተወራረሰ ባህሪ አላቸው። ለምሳሌ የኢኮኖሚ ግጭት አለ፤ ብዙ ሰው እንደሚለው የኑሮ ውድነት ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖር፤ ያለንበት ሁኔታ እንደሚያስረዳን አንዱ ሲሳካለት አንዱ ይወድቃል፤ ይህ የመደብ ግጭት ይሆናል። ይህ ነው የኢኮኖሚ ግጭት የሚባለው።

የፖለቲካ ግጭትም አለ። ይህ ማዕከል የሚያደርገው ትክክለኛ የአመራር አይነት ምን አይነት ነው? ከሚል ይጀምራል። መዋቅሮቹ፥ ያሉት ሂደቶች የሁሉንም ፍላጎቶች የሚያስተናግዱ ናቸው ወይ? አንዱን ወገን አሳትፎ ሌላውን አግልሏል ወይ ዴሞክራሲስ ምን ማለት ነው? ከአለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ዴሞክራሲ አለን ወይ? እንዴትስ እንፈጥራለን። እነዚህ ሁሉም የፖለቱካ ግጭት በሚለውን የሚያጠቃልሉ ናቸው።

የሀይማኖት ግጭትም ሊኖር ይችላል። አንዳንድ ቦታዎች ላይ በአንዳንድ አክራሪዎች ምክንያት የእምነት ቤቶች ሲቃጠሉ። በዚህ ምክንያት ሰው ሲናደድ አንዱ የሌላውን ሀይማኖት አሊያም እምነቱን የሚያከናውንበትን ቤተ እምነት ሲያወድም ይታያል። እዚህ ላይ በእርግጥ በሀይማኖት ምክንያት እንላለን እንጂ መነሻቸው ሀይማኖት ነው የሚል እምነት ግን የለኝም።

ምክንያቱም ሀይማኖት በእኔ አስተሳሰብ አያጋጭም። የትኛውም ሀይማኖት አያዳላም። ሀይማኖት ያስታርቃል፤ ያቀራርባል፤ ያከባብራል እንጂ አያጣላም። ነገር ግን አግባብ በሌላቸው የሀይማኖት ትርጓሜ በተለይ አክራሪዎች የማጥቂያ ምክንያት ሊያደርጉት ይችላሉ።

ሌላው የግጭት መነሻ በጎሳ ላይ የተመሰረተ እርስ በእርስ መጠላላት ነው። እዚህ ላይ ግልፅ መሆን ያለበት እና መረዳዳት የሚገባን ጉዳይ ዋናው ችግር ብሄሩ ወይም ጎሳ መኖሩ አይደለም። ብሄር ወይም ጎሳ ያለ እና የሚኖር ነው። በመሆኑም አንድ ሰው የእዚህ ጎሳ፣ የእዚያ ጎሳ አባል ለመሆን በምርጫ የሚደረግ አይደለም። ይህ እድል በሰጠችህ ትወለዳለህ፡፡ ጎሳና ብሄር በራሱ አያጣላም አያጋጭም። የሚያጋጨው ጎሰኝነትና ብሄርተኝነት ነው።

ጎሰኝነት ወይም ብሄርተኝነት ማለት አንዱ ከአስተሳሰቡ ጀምሮ እርሱ የበላይ ሆኖ ሌላውን መናቅ፥ ማሳነስ ሌላውን መጠየፍ የራስን ብቻ ከፍ አድርጎ ማየት፡፡ የእኔ ጎሳ ወይም ወገኔ ካልሆኑ በስተቀር ሌሎቹ የእኔን እድል እንዳይካፈሉ በሩን መዝጋት ነው -ጎሰኝነት።

የሚያጣላው ጎሰኝነት ነው እንጂ ጎሳ በመኖሩ አሊያም አንድ ሰው ከሌላ ጎሳ ስለተዋለደ ሌላ ቋንቋ ስለተናገረ ብቻ ሰው አይጣላም። እንዲያውም ብዙ የጎሳ አይነቶች መኖራቸው ጌጥ ነው።

ጎሳ እና ብሄር ወደ በሄርተኝነትና ወደ ጎሰኝነት እንዳይቀየር በጥበብ መያዝ አለበት። ከዚህ አኳያ ስትመለከተው ሌላ የግጭት ምንጭ ምንድን ነው ብትል ጎሰኝነትና ብሄረተኝነት ነው። በአገራችን ያሉ የግጭት ምክንያቶች ምንድን ናቸው ካልን በርካታ ናቸው። እነዚህም በዋናነት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሀይማኖታዊና ጎሰኝነት እና ብሄርተኝነት ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- በርካታ አስተያየት ሰጪዎች በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ገዝፎ የሚታየው የፌዴራል ስርዓቱ ያመጣው የጎሳ ክፍፍል ነው ይላሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ረገድ ምን አስተያየት አለዎች?

ፕሮፌሰር እስቅያስ፡- እንግዲህ እዚህ ላይ ሁለት የሚሳከር ነገር አለ። ይህ ጉዳይ ግልፅ መሆን አለበት። ይህ ካልሆነ ግን ግልፅነት ይጓደላል። እዚህ ላይ ብሄርን እና ብሄርተኝነትን እኩል አድርጎ ማየት የሚያመጣው ጣጣ ነው። ጎሳ እና ጎሰኝነትን የማያውቁ ግለሰቦች የሚፈጥሩት አለመረዳት ነው። በግልፅ እንዳነሳሁልህ የጎሳ ወይም የብሄር መኖር ያመጣው ምንም አይነት ችግር የለም። እዚህ ላይ የተመሰረተ እኔ እበልጣለሁ፤ የሌላውን እድል እዘጋለሁ፤ ይህን እጠየፋለሁ፤ ይህን አላከብረውም፤ የሚለው ነው የግጭቱ ዋና መንስኤ።

እናም ዋናው ጥያቄ የተለያዩ ብሄሮች ባሉበት ሁኔታ ውስጥ ከብሄር ወደ ብሄርተኝነት ነገሮች እንዳይሄዱ ምን አይነት ሁኔታዎች እንፈጥራለን። ምን አይነት ነገሮች እናመቻቻለን? ምን አይነት ስርዓቶች አሊያም አወቃቀሮች፣ ምን አይነት ማረጋገጫዎች እናደርጋለን የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው።

አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ አይነት ጎሰኝነትና መከፋፈል የመጠላላት የአንድነት ስሜት ሲደክም ያለንን የጋራ ችግር እንፍታው ሲባል እንኳ በጣም ይከብዳል። ግን የተለያየ ብሄር ቢኖር ደግሞም እነዚህን ብሄሮች መለስ ብለን ስናይ አንድ የሚያደርጋቸው ብዙ ነገር አለ።

እናም ብሄር ላይ ብቻ ካተኮርን የሚያስተሳስ ራቸው ላይ ካላተኮርን ወደ ግጭት ሊወስደን ይችላል። ምክንያቱም ያለን አንድነት ተበተነ ማለት ነው። ስለዚህ አሁን ያለው አንገብጋቢ ጥያቄ ወደ ብሄር እና ጎሳ ያለው አቋም መጠላላትና መቃቃር እንዲሁም ወደ መቆራረስ እንዳይሄድ አንድነታችንን የሚያጎላምስ፣ ለአንድነታችን መንገድ የሚከፍት አንድነታችንን የሚያጠናክር እድል እና ሁኔታ መፍጠር አለብን።

በእኔ በኩል ያለው ሁኔታ ይህ ነው። ምናልባት ያሰጋናል ብሎ ጎሳና ብሄርን ምክንያት ማድረግ እኔ የሚገባኝ ምንድን ነው፤ ምነው የሚያለያየን ላይ ብቻ አተኮርን? የሚያገናኘንስ ላይ ለምን አናተኩርም። ለምሳሌ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሲከበር፥ የሰንደቅ አላማ ቀን፥ ሌሎችም እንደዚሁ ነው። በእነዚህ በዓላት እያንዳንዱ ሰው ብሄሩ ያለውን ሁሉ መልካም ነገር ያስተዋውቃል፤ ልዩነት ምን ያህል ውበት እንደሆነ ይረዳል፡፡ የሌላውንም ይገነዘባል፤ በመጨረሻም የራሱ እንዲከበር እንደሚሻው ሁሉ የሌላውንም ያከብራል። ይህ ሲሆን ደግሞ ጎሳ እና ብሄር የግጭት ምክንያት መሆኑ ይቀራል። በምትኩም መከባበር እና መቻቻሉ እየጠነከረ ይመጣል።

እያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብ እና ጎሳ የራሱን ባህል በተለይ ደግሞ ሙዚቃውና ዳንሱ፥ ባህላዊ የሆኑት የራሱ መገለጫ የሆኑ ቁሳቁሶቹን ይዞ ሲታይ፥ የሌላውንም ሲያይ ብሄሮች ከሌሎች ብሄሮች ጋር፤ ባህሎች ከሌሎች ባህሎች ከኢትዮጵያዊነቱ ጋር ተዳምሮ የሚያደርገውንም ባህል አብሮ ቢያንጸባርቅ በተለይ ደግሞ የእኔ ብቻ ነው ትክክል እና የተሻለ ከሚለው አስተሳሰብ ወጥቶ ወደ የሚያስተሳስረን ጉዳይ ስንመጣ የተሻለ አስተሳሰብ እንዲኖረን ይረዳናል። አንድነት ጥንካሬ ነው። ይህም እድል ይሰጠናል። ስለዚህ ልዩነታችን ላይ ብቻ አናተኩር። የሚያገናኘንም ላይ ቆመን ችግራችንን እንፍታው፤ የዚህን ጊዜ ይበልጥ የተሻለ መልስ እናግኛለን።

አዲስ ዘመን፡- የሰላምና የእርቅ ጉዳይ ባለቤቱ ማን ነው ይላሉ?

ፕሮፌሰር አስቅያስ፡- ባለቤቱ ማን ነው የሚለው ጥያቄ ግልፅ አይደለም። እኔ እንደገባኝ ከሆነ በመጀመሪያ ደረጃ የእዚህ ጉዳይ ባለቤት የተጋጩት ወገኖች ናቸው። ተጋጭተዋል፤ ተጎዳድተዋል፤ በተለይ ደግሞ የጠበቀ ዝምድና ካላቸው ያ ዝምድና አጓጉቷቸው መጎዳዳቱን ወደ ኋላ አድርገው፤ ያለፈውን ትተን እንደገና እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደ ፊት አብረን እንገንባ፤ የነበረንን አንድነት እንደገና እንመስርት የሚል ነው የእርቅ ትርጉሙ።

በእርግጥ የሰላምና የእርቅ ባለቤቶቹ የተጋጩት ናቸው። ብዙ ጊዜ የህብረተሰብ ግጭት በሚሆንበት ወቅት በሁለት ወገኖች ብቻ አይቆምም፡፡ ለምሳሌ ባልና ሚስት ይጣላል። እነዚህ አካላት በተፈጠረው የግጭት ምክንያት ብዙ ይጎዳዳሉ። በንግግር ብቻ ሳይሆን በዱላ ጭምር ይጎዳዳሉ።

ይሁን እንጂ ባልና ሚስት ሲጣላ ስቃዩ በሁለቱ አካላት ብቻ ተገድቦ አይቀርም። ቤተሰብም ይሰቃያል። ይህ ማለት የባልም ሆነ የሚስት ቤተሰቦች ተጎጂዎች ይሆናሉ ማለት ነው።

የእነዚህ ሰዎች ግጭት ሊሰፋም ይችላል። ሀይማኖተኞች ቢሆኑም እንኳ የቤተ ክርስቲያን ወይም የመስጊድ ሰዎች መሆናቸው አይቀሬ ነው። እነዚህ የተጋጩ ሰዎች በእርቅ መፍታት ባለመቻላቸው ቤተ ክርስትያን ወይም መስጊድ ያፍራል።

ሀይማኖታችን የሚላቸው ስርዓቶ ሊከበሩ አልቻሉም፤ በሚል ተቋም ብቻ ሳይሆን አስተማሪም ጭምር ያፍራል። ስለዚህ በባልና በሚስት መካከል ለሚኖረው እርቅ ባለቤቶቹ ልጆች እና የሁለቱ ወገኖች ቤተሰቦች ናቸው፤ ጎረቤቶችም ናቸው፤ የእምነት ቤቶቹ ናቸው። እንዲህ አንዲህ እያለ እየሰፋ ይሄዳል።

በአገር ደረጃ ከሆነ እንግዲህ ፓርቲዎች ከተጣሉ ይህማ የእነሱ ጉዳይ ነው ብለን ልንተወው አንችልም። በፓርቲዎች መጣላት ከእነሱ ጀርባ ያሉ ደጋፊዎችና ቤተሰቦቻቸውንም ጭምር ይመለከታል። ወደ ላይም ሆነ ወደታች የማይነካው አይኖርም። ስለዚህ ሁላችንም ለእርቅና ለሰላም ጉዳይ ባለቤቶች ነን።

የእርቅ ጉዳይ በእኔ እምነት እና ነፃ ሆነን ስናስበው እርቅ አንዱን ጠቅሞ ሌላውን የሚጎዳ፤ ከእርቅ የማይጠቀም ሰው አለ ቢባል ሀሰት ነው። በዚህ ረገድ አንዱ ተጠቅሞ ሌላው የሚጎዳ ከሆነ እውነተኛ እርቅ አይደለም። በመሆኑም የእርቅ ባለቤት ሁላችንም ነን።

በአገር ደረጃ ያለ እርቅ የተጋጩት ሁለት ወገኖች ብቻ አይደሉም የእርቅ ተጠቃሚዎች፡፡ ለምሳሌ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እርቅ ካለ ሰላም ይወርዳል፡፡ በዚህ ወቅት ደግሞ ሁላችንም ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡ ሁላችንም ሰላም ስናገኝ ሰላም ይመጣል፡፡ ንግዱም ግብርናውም አደገ ማለት ነው፡፡ ኢኮኖሚውም አደገ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ባለቤቱ ማን ነው ብትል ሁሉም ዜጋ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባለቤት ያልሆነ የለም፡፡ እርቅ ሁሉንም ችግር ለመፍታት የሚያስችል መንገድ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እንደ አለም አቀፍ የሰላምና እርቅ አደራዳሪ ባለሙያ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የነበሩ ግጭቶችን ታዝበዋል፤ ግጭቶችንም በሰላም በመተካት ችግሮችንም ፈተዋል። በዚህ ረገድ ያገኙትን ልምድ ቢያካፍሉን?

ፕሮፌሰር እስቅያስ፡- በተለያዩ አገራት ግጭቶች ተከስተዋል አድገውም ብዙ ጥፋት አድርሰዋል፡፡ በግጭት ወቅት በአንድ ሰው ላይ የደረሰውን ችግር ምክንያቱ ምንድን ነው? በግጭቱ ሳቢያ የተከሰተ ጉዳት አለ፡፡ በዚህም የተነሳ ከዚህ ሰው ምንድን ነው የምማረው ብሎ ማሰብ ተገቢ ይሆናል፡፡

አሁን እነ ሩዋናዳ፣ ኬንያ ላይቤሪያ ቡሩንዲ እና ልሎችም አገራት ላይ የደረሰውን ግጭቶች ለመፍታት ብዙ ሰርተናል፡፡ ሩዋንዳ እና ቡሩንዲ ደቡብ አፍሪካ የተፈጠረው በእነሱ ብቻ የተፈጠረ አይደለም፡፡ ተደጋግሞ ተደጋግሞ ብዙ አገራት ወስጥ ታይቷል፡፡ ካምቦዲያ ኤሽያ ውስጥ ጓቲማላ ውስጥ፤ ደቡብ አምሪካ ውስጥ በአሜሪካ ራሱ፤ በሪድ ኢንዲያን፣ በአፍሪካን አሜሪካን ውስጥ ሁሉ አለ፡፡ ግጭቶቹ የሚደጋገምበት ምክንያት አንዱ ከሌላው ስህተት ባለመማር ነው፡፡

አሁን ሩዋንዳ ውስጥ እንዲያ ያስተላለቃቸው አንዱና ዋናው የብሄር ጉዳይ ነው፡፡ እኛ አገር ውስጥ 80 የሚደርሱ ብሄሮች አሉ፡፡ ይህን ያህል በዝተን ግን ለእልቂት አልተዳረግንም፡፡ በሩዋንዳ ግን ሁለት ብሄሮች ብቻ አሉ፡፡ በእነዚህ ብሄሮች ታይቶ የማይታወቅ አሰቃቂ ግድያ ተፈጸመ፡፡ ሶስት ወር ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ስምንት መቶ ሺ ቱትሲ አለቀ፡፡

ይህ ለምን ሆነ ብለህ ስታስብ በወቅቱ የነበረው መንግስት በብሄርተኝነት በጣም የላቀ ስለነበረ ያ መንግስት ለሁትሱ ብቻ ተቆርቋሪ በመሆኑ ቱትሲዎች መጥፋት አለባቸው በሚል ውሳኔ ውስጥ ገቡ፡፡ ስለዚህ በስመ ቱትሲ ብዙ ሰው አለቀ፡፡

ይህ ሲሆን አንደኛ ጊዜ በታሪካቸው፣ በአሰፋፈራቸው ተመሳሳይ በሀይማኖታቸው ተመሳሳይ ሁለተኛ በጋብቻም ተሳስረዋል፡፡ በወቅቱ ሁቱና ቱትሲ የሚለውን በመልክ ለመለየት ስላልተቻለ መታወቂያቸው ላይ በተጻፈው በመለየት ብዙ ጥፋት ተፈጽሟል፡፡ ማንነታቸውን በገንዘብ በመቀየር ከሞት የተረፉ እንደነበሩ ለማየት ችያለሁ፡፡

ይህን ሁሉ ስናይ ምንድን ነው ከዚህ የምንማረው ብሎ ለሚቀርበው ጥያቄ የሚገኘው መልስ ነው ትልቁ ቁምነገር፡፡ እንደ ሩዋንዳ አይነቱ ብሄር ላይ የተመሰረተ ግጭት መጨረሻው ይህን የመሰለ ጥፋት ነው፡፡ ስለዚህ ወደ እዚህ ከመድረሱ በፊት ከዚህ መሰሉ ስህተት ተምሮ መጓዝ ነው ዋናው፡፡ ይህን መሰሉ ግጭት የትም ቢነሳ ወዳልተፈለገ መጠላላት እንዳይሄድ ምን መሰራት አለበት ሲባል የጉዳዩን አያያዝ ማሳመር ይቀድማል ማለት ነው፡፡

በዚህ መሰረት ሩዋንዳ ውስጥ የሰራሁት በእርቅ ስራ ነው፡፡ በዚህች አገር ያሉ ሁለት ብሄሮችን በማስታረቅና በዚህም መሰረት የቀድሞው ዝምድናቸውን እንዲመሰርቱ እና እንዲያጠናክሩ የማድረግ ስራ ነው የሰራነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በሩዋንዳ በአሁኑ ወቅት ይህ ችግር ተቀርፎ ተረጋግተው እየኖሩ ነው፡፡ ምን አይነት ስራ ቢሰራ ነው፤ የእርቀ ሰላሙ ስራስ ይዘቱ ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር እስቅያስ፡- የሩዋንዳ አንዱ ጉዳይ ቅድም እንዳልኩህ ጎሰኝነት ላይ ማተኮር አንድነታችንን አድክሞታል፡፡ በወቅቱ ሩዋንዳዊያን ነን ከማለት ፈንታ ሁቱና ቱትሲዎች እየተባባልን ኖረናል፡፡ ነገር ግን ሁላችንንም የሚያስተሳስረን ማንነት አለን ያም ማንነት ሩዋንዳዊነት ነው ብለው ተግባቡ፡፡

ስለዚህ ይህን ሩዋንዳዊነት ትርጉም ያለው ማንነት ለማድረግ ምን ማድረግ አለብን በሚል መንግስቱ ብዙ ጥረትና ስራ በመስራቱ ነው፡፡ በመሆኑም አንዱና ዋናው ዜግነት ሁሉንም የሚያስተሳስር ማንነት በእውነትም በተግባር ጭምር እንዲያስተሳስር ማድረግ በመቻሉ ነው፡፡

በዚህም መሰረት የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ ኢኮኖሚያዊ መብቶችንም ጭምር በማስከበር ፍትህ በመስጠት መልካም አስተዳደርን ማስፈንና ብሶት ሲኖር ቶሎ መፍትሄ የሚሰጥበት አሰራር ሲኖር ነው ሰላምና መረጋጋቱ የሚጠናከረው ፡፡ ያንን ካደላደልን ወንድምና እህትነቱን ያጠናክራል ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ይህን አይነቱን ችግር እንዴት ነው የምንፈታው በተለይ የሁቱና ቱትሲነት ላይ ብቻ ከማሰብ አልፎ ሩዋንዳዊ ነኝ፡፡ የሩዋንዳዊነት ጥላ ለሁላችንም ቦታ አለው ብሎ እንዲያምን ማድረግ አለብን ብለው ሩዋንዳዊያኑ ብዙ ስራ ሰርተው ዛሬ ተቀይረዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻም ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ አድሉን ልስጥ፡፡

ፕሮፌሰር እስቅያስ፡- እርቅም ሰላምም ስንል ወደ ሰላም ለመምጣት መንገዱ ደግሞ ውይይት ነው፡፡ ውይይት ስንል ደግሞ የራሱ ሂደቶች አሉት፡፡ ወደ እርቅ ሊመራ የሚችለው ውይይት የሚያደማምጥ መሆን አለበት፡፡ ውይይት እኔ የምለውን ሀሳብ ብቻ ለመግፋት በመብለጥለጥም ሆነ በምላስ ሊገለጽ ይችላሉ፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡ አስር ብጮህ ሌላኛው ወገን በእኔ ሀሳብ እምነት ከሌለው በሀይል የምጫን ከሆነ ተቀባይነት የለውም፡፡ ውሎ አድሮ ሌላ ችግር ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ ውይይት ከተባለ የሚያደማምጥና የሚያቀራርብ ሊሆን ይገባል፡፡

ተፈጥሯችንን ተመልከት፤ ፊታችን ላይ ስንት አፍ አለን፤ አንድ፡፡ ስንት ጆሮ አለን ሁለት፡፡ በመሆኑም ተፈጥሮ ራሷ ልትነግረን የምትፈልገው ነገር አለ፡፡ የምትናገሩትን ያህል እጥፍ አዳምጡ ነው መልእክቱ፡፡ እኛ ጋር የጎደለው ውይይት ተፈጥሮ የማዳምጠው እኔ የምለውን ብቻ ተቀበሉ የሚል ነው፡፡ ይልቅ እስኪ ላዳምጥህ የሚለውን እንዘነጋለን፡፡ ማዳመጥ ራሱ ከልብ አለ በአንድ ጆሮ ሰምቶ በአንዱ ማፍሰስ አለ፡፡

ችግሩን ለመፍታት እስኪ እዛ ሰውዬ ያጋጠመው ችግር ላይ ሆኜ ብሶቱን ላዳምጥ፤ ሙሉ በሙሉ እንኳ ባይሆን ልቤን ልክፈትና ልረዳው ሲል እውነተኛ መደማመጥ ይመጣል፡፡ እውነተኛ ውይይት ማለት ይህ ነው፡፡ በመሆኑም ውይይት ስንል ለመጯጯህ ሳይሆን ለመግባባት ነው፡፡

መግባባት ብዙ ጥበብ የያዘ ነው፡፡ መግባት ከሚለው ቃል የመነጨ ነው፡፡ በመሆኑም አንዱ ሀሳቡ በአንዱ ውስጥ ሲገባ ማለት ነው መግባባት የምንለው፡፡ አንድ ሰው ሌላኛው ሰው ልብ ውስጥ ገብቶ መልካሙን ቦታ ሲያገኝ ነው መግባባት የሚመጣው፡፡ ሌላው አንዱ ሰው በሌላኛው ልብ ሲገባ ሚፈጠር ነው፡፡ ይህ ሲሆን መደመጥ ይመጣል ማለት ነው፡፡

በመጨረሻም ውይይት ማለት መግባባት ነው፤ መግባባት ደግሞ ሰላም ነው፤ ሰላም ደግሞ እርቅ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ይጠቅማል እንጂ ሰላምና እርቅ ማንንም አይጎዳም፡፡ በመሆኑም የሁለታችን ችግር ሲፈታ ሰላም ይመጣል፡፡ ውይይጥ እና እርቅ እዲጎለብት ቦታውን ማመቻቸት፤ ልብንም ክፍት ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ከልብ በሚሆን ውይይት ላይ ሁለቱም ወገኖች አሸናፊ ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግ ናለሁ፡፡

ፕሮፍሰር እስቅያስ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

 

ሐብታሙ ስጦታው

 

 

Published in ፖለቲካ

ለመስኖ ልማት የሚውል የመሬት አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ ከኅብረተሰቡ ትብብር ይጠበቃል፤

 

የርብ ግድብ ግንባታ በ 2002 .ም ቢጀመርም ግድቡ የሚያርፍበትና ውሃው ተገድቦ የሚቀመጥበትን መሬት ዝግጁ በማድረግ ድንበር ለማስከበር ሁለት አመት ወስዷል። በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ ስራ ከ95 በመቶ በላይ የተከናወነ ሲሆን፤ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ስራ እንዲጠናቀቅ የተቀመጠለት ጊዜ ደግሞ በያዝነው አመት መጋቢት መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ዛሬም ፕሮጀክቱን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ የቀሩት የግንባታ የማጣሪያ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም፤ ከግድቡ ግንባታ ውጪ ያሉ የውሃ መውረጃና ተዛማች ስራዎችን ለመስራትና በተለይ ደግሞ በመስኖ የሚለማውን መሬት የማቅረቡ ስራ በሚፈለገው ደረጃ እየተካሄደ አይደለም፡፡ ይህም በመሆኑ ለታቀደው የመስኖ ልማት ስራ ስጋት ሆኗል። በቅርቡም የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር በክልሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረገው የመስክ ጉብኝትና የውይይት መድረክ ችግሮቹን በማንሳት በመፍትሄዎቹ ላይ መክሯል።

አቶ ተመቸው መካሻ በርብ መስኖ ፕሮጀክት በመሬት ልማትና አጠቃቀም ቢሮ ስር የማህበራዊ ልማት ባለሙያ ናቸው፤ በርብ ግድብ እንዲለሙ በእቅድ የተያዙት ቦታዎች ከግድቡ ከ40 እሰከ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ሲሆን በባታ አቀማመጣቸው የላይኛውና የታችኛው ተብለው የተለዩ መሆናቸውን ይናገራሉ። የታችኛው ተብለው የተለዩ የመስኖ መሬቶችን ለልማት ዝግጁ ለማድረግ በሚሰሩ ስራዎች ላይ እየገጠማቸው ያለውን ችግር እንዲህ ያብራራሉ። ከመሬት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከአርሶ አደሩና ከኮንትራክተሩ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ።

ቀዳሚው በኮንትራክተሮች በኩል መሬት በጊዜ አይቀርብም የሚል ነው፤ ለዚህ ምክንያቱ የመሬት ጥያቄው በወቅቱ ያለመቅረቡ ሲሆን ይሄ ሊፈጠር የቻለው ደግሞ ዲዛይኑ ከስር ከስር ስለሚሰራ የሚፈጠር መዘግየት ነው። የዲዛይኑ ዘግይቶ መምጣት ደግሞ በነባር አርሶአደሮቹ ይዞታ ስር እያለሙት ያለውን መሬት ተገቢውን ካሳ ከፍሎ ለልማት ዝግጁ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በአግባቡና በተፈለገው ፍጥነት እንዳይጠናቀቁ መሰናክል ሆኗል። ይሄ ችግር ባለበት ሁኔታ ከህዝቡ የሚቀርቡ ጥያቄዎች በአግባቡ ሳይፈቱና ውሳኔ ሳያገኙ የኮንትራት ስምምነቱ ስለሚፈረምና ኮንትራክተሮቹ ስራ መጀመር ስለሚፈልጉ መሬቱን በወቅቱ መረካከብ ባለመቻሉ ቅሬታዎች ይቀርባሉ ።

ሌላው በኮንትራክተሮች በኩል ከመሬት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ከተሰጠው በላይ አልፎ የመሄድ ችግር እንዳለ በአርሶ አደሮች በኩል የሚነሳው ቅሬታ ነው። ከዚህም ባለፈ ሲጀመር የመሬት ጥያቄው መቅረብ የነበረበት በአካባቢው ተገኝቶ ያለውን ሁኔታ በማገናዘብ ሊሆን ይገባ ነበር። ነገር ግን ይሄ ባለመደረጉ በቢሮ ብቻ የሚሰራ በመሆኑ አስፋልትን፣ የኤሌክትሪክ ፖልን የውሃ ጉድጓድን ጨምሮ በፕላን ውስጥ ተካተው የሚመጡበት ሁኔታ አለ።

እንደ እዚህ አይነት ችግር ሲያጋጥም በቀረበው ዲዛይን ስራውን ማስቀጠል ስለማይቻል ዲዛይኑን እንዲያስተካክሉት ላዘጋጁት አካላት ተመልሶ ይላክላቸዋል። ይሄ በራሱ የሚፈጀው ጊዜ ቀላል ካለመሆኑ ባሻገር ውጤቱም አጠቃላይ ፕሮጀክቱ ስራ ላይ መዘግየትን ሲያስከትል መቆየቱን አቶ ተመቸው ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በጥናት ችግር ለውሃ አቅርቦት ስለማይመቹ ሊለሙ የማይችሉ መሬቶች በዲዛይን የተካተቱ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በቦታ አቀማመጡ የላይኛው የመስኖ ልማት ተብሎ በተለየው አካባቢ ከተለዩት የልማት መሬቶች ሊለማ የሚችል ሰባት ሺ ሄክታር መሬት ደግሞ መስኖ ቦይ ስላልተዘጋጀለት ሳይለማ ቀርቷል። አሁን ደግሞ ይሄው ጥናት በቦታ አቀማመጡ የታችኛው ተብሎ ከተለየውና በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት ሳይካተት ቀርቷል። በዚህም በአቀማመጡ ሜዳማ የሆነ፣ ከአሁን በፊት አርሶ አደሮች በባህላዊ መስኖ ይጠቀሙበት የነበረና ከወንዙ ዳር የሚገኝ 500 ሄክታር የሚደርስ መሬት በዲዛይኑ አልተካተተም። ይህንን ቦታ በማካተት ቦታውን ለልማት ለማዋል ውሃውን የሚያደርስ ካናል የማዘጋጀት ስራ መሰራት የነበረበት ቢሆንም በዲዛይኑ የተቀመጠ ነገር ግን የለም። አሁንም ቦታዎቹን ለይቶ በዲዛይኑ ማካተት የሚቻልበት ሁኔታ ስላለ ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተው እንደገና በማየት ውሳኔ ሊሰጡበት እንደሚገባ አቶ ተመቸው ጠቁመዋል።

አቶ ተመቸው፣ የዚህ ሁሉ መነሻ በአግባቡ ጊዜ ተወስዶ ጥናት አለመካሄዱ እንደሆነም በመጠቆም፤ በዚህ ወቅት ኮንትራክተሩ ማሽን አስገብቶ ስራ ስለጀመረ ወደኋላ ተመልሶ ዲዛይን ይሰራ ማለት እንደሚያስቸግር ይናገራሉ፡፡ ሆኖም አጠቃላይ ስራው ባለመጠናቀቁ ከስር ከስር አስተዳደራዊ ውሳኔ እየሰጡ የማቻቻል ስራ መስራት እንደሚገባና የሚለሙትን መሬቶች ማካተት እንደሚቻልም አስረድተዋል፡፡

የውሃ መሰኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ገርባ በበኩላቸው፣ የመሬት አቅርቦት በተለያየ ምክንያት የሚዘገይበት ሁኔታ እንዳለ በማንሳት፤ ፕሮጀክቱ ሊጠናቀቅ አጭር ጊዜ የቀረው በመሆኑ ችግሩ በተቻለ ፍጥነት ከመሰረቱ ሊፈታ እንደሚገባው ተናግረዋል። በተለይ ካሳ በተከፈለባቸው ቦታዎች ላይ መልሶ በመስፈር የማረስ ነገር በመኖሩ እስኪሰበሰብ መጠበቅ አንዱ ችግር እንደነበርም ጠቁመዋል።

የካሳ ክፍያን ጨምሮ በሎጀስቲክ፣ በሰው ሀይልና ተዛማጅ ጉዳዮች መዘግየት እንደነበርም የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በአሁኑ ወቅት የኮንትራክተርና የማማከር አቅማችን የተስተካከለ በመሆኑ በቀጣይ አጭር ጊዜ ውስጥ ይህንን ለመቅረፍ የሚያስችል አቅም ላይ እንዳሉ አስረድተዋል። በዚህም ሙሉ በሙሉ የርብን ሦስት ሺ እና የመገጭን አራት ሺ የመስኖ ግንባታ መሰረተ ልማቶች አከናውኖ ለማስረከብ እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ውሀው ከግድቡ ወደሚለሙት መሬቶች የሚወርድበት የወንዝ ስራ ረጅም ኪሎ ሜትር የሚሄድ ሲሆን ሰፊ መሬት ይወስዳል ተብሎ እስካሁን መሬቱ የተዘጋጀ እንዳልነበር ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አሁን ግን በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በኩል ካሳው ተከፍሎ መሬቱ እንዲዘጋጅ መወሰኑን አስረድተዋል። ይህንንም ለመተግበር ለአካባቢው የገጠር መሬት አስተዳደር ጥያቄ እንዲቀርብ ደብዳቤ መቅረቡንና በቅርቡም መሬቱ ለግንባታ ዝግጁ እንዲሆን አስፈላጊው ሁሉ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የፕሮጀክቱን ስራ እያጓተተው ያለው የመሬት አቅርቦትና ከካሳ ጋር የተያያዘው ችግር ቀዳሚ እንደሆነ በመግለፅ፤ ለዚህም በክልሉ በኩል አስፈላጊው እንደሚደረግ የተናገሩት ደግሞ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ናቸው። እስከ ዛሬ ለፕሮጀክቱ መጓተት እንደ ችግር የሚነሳው የዲዛይን ስራው ነበር ያሉት የክልሉ ፕሬዚዳንት፤ አሁን ይህ ችግር እየተፈታ እና ዲዛይን የሚሰሩት ባለሙያዎች ስራቸውን ካጠናቀቁ በዚህ መሰረት የካሳ ግምቱን የመክፈሉና መሬቱን ለኮንትራክተሩ የማስረከቡ ስራ በአጠቃላይ የፕሮጀክቱ ሂደት ላይ ክፍተት እንደፈጠረ አስረድተዋል።

በመሆኑም በክልሉ በኩል የሚመለከታቸው አካላት በተለይ የመሬት አስተዳደር ቢሮ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ካሳውን የማጥናትና መሬቱን የማስረከብ ስራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል። የውሃ ሀብት ሚኒስቴርም የካሳ ግምት ተገምቶ ከሄደለት በኋላ ክፍያ ለመፈጸም የሚዘገይ መሆኑን በማንሳት ይህንን ሊያስተካክል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው፤ ሲጀመር የመሬት አቅርቦትና የግንባታ ስራው በአንድነት እንዲሰራ የተደረገው ጊዜ ለመቆጠብ ታስቦ መሆኑን አስታውሰው፤ ነገር ግን አርሶ አደሩ በወቅቱ እንዲነሳ ባለመደረጉ በአሁኑ ወቅት መሬቱ በሰብል የተሸፈነ በመሆኑ ሰብሎቹ ሳይነሱ ወደ ስራ መገባት እንደማይቻል ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ቦታዎች ላይ አርሶ አደሮቹ ከቦታቸው ከተነሱም በኋላ ተመልሰው የለቀቁትና ካሳ የበሉበት ቦታ ላይ ዘር የመዝራት ነገር እየተከሰተ በመሆኑ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት የህብረተሰቡ ትብብር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት የሚለማው መሬት በዲዛይን ተለይቶ አልቋል፤ የሚቀረው ስራ የመሬት ርክክብ፣ የካሳ ከፈላና የውሃ መውረጃዎችን የመገንባት ስራ ብቻ እንደሆነ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ዲዛይኑ አልቆ መሬቱ ተለይቶ ካሳና ምትክ መሬት የማዘጋጀቱን ስራ በጊዜ ማጠናቀቅ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።

ሚንስትሩ ጨምረው እንደተናገሩት፤ በርብ ግድብ በመስኖ ለመልማት የተዘጋጀው መሬት ግድቡ ካለበት እስከ 50 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ እንደሆነና ፤ ውሀው በወንዝና በቦይ አማካይነት እንደሚደርስ ገልፀዋል፡፡ ወንዙ በሚያልፍባቸው ነገር ግን በመስኖ ልማቱ እቅድ ውስጥ ባልተካተቱ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችንም ተጠቃሚ ለማድረግ ውሃ መሳቢያ ጄነሬተር ለመጠቀምና የከርሰ ምድር ውሃ ለማውጣት እቅድ መያዙንም ጠቁመዋል።

የርብ ግድብ ሲጠናቀቅ 230 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ በመያዝ 3 ሺ ሄክታር መሬት ማልማት የሚችል ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግድቡ ከያዘው ውሃ 18 ሜትር ኪዩብ በሰከንድ ለገበሬው የመስኖ አገልግሎት በመለቀቅ ላይ ነው። ይሄም የመስኖ ልማት ለጀመሩ የአካባቢው አርሶ አደሮች ሙሉውን የበጋ ወቅት በቂ ውሃ ሳይቆራረጥ እንዲደርሳቸው የሚያስችል እንደሆነ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

 

ራስ ወርቅ ሙሉጌታ

 

Published in ኢኮኖሚ
Saturday, 04 February 2017 18:42

ሕጉ ጠንካራና ተፈጻሚ ይሁን

 

የሕግጋት መላላትና ተፈፃሚነት ማጣት በመላው ዓለም አገራት ውስጥ የሚታይ ችግር ነው፡፡ አነሳሳችን ስለ ሁሉም ሕጎች ለመናገር ሳይሆን በተለይ ከምግብ ደህንነትና መድኃኒት አስተዳደሩ ከሙስና ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ለማተኮር ነው፡፡ በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት 2017 መግቢያ የመጀመሪያ ቀናት (Jan,3) ቻይና ውስጥ ትልቅ መንግሥታዊ ስብሰባ ነበር፡፡ በምግብ ደህንነት ላይ ያተኮረና የአገሪቱ ዋና ዋና መሪዎች ማለትም ፕሬዚዳንቱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገኙበት ነው፡፡

ፕሬዚዳንቱ ዘ-ጂንፒንግ እንደተናገሩት «ከምግብ ደህንነት ጋር በተያያዘ ትኩረታችን ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን በላይ ቁጥር ካለው የቻይና ሕዝብ ጤንነትና ሕይወት ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ስለሆነ በዚህ ላይ የበለጠ መሥራት አለብን» ብለዋል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት የቻይና መንግሥት የምግብ ደህንነትን ይዞታ ለማሻሻል ታላቅ ጥረት አድርጎ መሻሻሎች የተገኙ ቢሆንም አሁንም ብዙ ቀሪ የቤት ሥራዎች አሉብን ብለዋል፡፡ በየደረጃው የሚገኙ ባለሥልጣኖች በሙሉ ጠንካራ መለኪያና የማያወለዳ ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ የምግብ ደህንነትን የሚቆጣጠሩ የባለሞያዎች ቡድኖችም ተቋቁመው በጉዳዩ ዙሪያ ያሉትን ሕጎች ይዘት እየመረመሩ የሚያጠናክሩና የሕጉንም ተፈፃሚነት የአስፈፃሚዎችን አቅም እየገመገሙ እንዲያሻሽሉ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ-ኬኪያንግ በበኩላቸው የክልል መንግሥታትና የከተማ አስተዳደሮች የምግብ ደህንነት ሂደቶችን አስተማማኝነት ለማረጋገጥና የቁጥጥር ሥርዓቱን ለማጠናከር ማንኛውንም ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥብቅ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ «የምግብ ደህንነት የሚጀምረው ከምንጩ (ከጅማሪው) መሆን እንዳለበትና በሂደቱ ውስጥ የሚታዩ መስተጓጉሎች ደግሞ ከፍተኛና የሚቆጠቁጥ ቅጣት ማግኘት አለባቸው፡፡ የሕዝባችን ጤንነት ጉዳይ ነው፤ የሕዝባችን ሕይወት ጉዳይ ነው መላላት የለብንም፡፡ ሕጉ መሻሻል አለበት፤ ይበልጥ መጠናከር አለበት፡፡ ከምግብ ደህንነት ጋር በተያያዘ ወንጀል በሚፈጽሙት ላይ ርህራሄ ሊኖረን አይገባም» በማለት ነበር ለጉዳዩ ትኩረት መስጠታቸውን ያረጋገጡት።

የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የመንግሥት ምክር ቤት የምግብ ደህንነት ኮሚሽን ኃላፊ የሆኑት ዛንግ ጋኦሊ በበኩላቸው የአገራቸው የምግብ ደህንነት ይዞታ በተግዳሮት የተሞላና በጣም ውስብስብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ እርሳቸውም «የምግብ ደህንነት ሕጎች ይበልጥ እንዲጠናከሩ የምግብ ሕገወጥነቶችን ለመዋጋት አቅማችን መጎልበት አለበት፡፡ በተለይም የምግብ ግብዓቶችን ጥሩውንና መጥፎውን እየደባለቁ/ እየቀየጡ/ (Food Adulteration) የምግብን ጥራት በመቀነስ የሚሰሩ ወንጀሎችን የቅጣት መጠንና ቆጥቋጭነት በጣም አስፈሪ ማድረግ አለብን፡፡ የሕግ የመከታተል አሠራራችን ከእስካሁኑ የበለጠ ሆኖ ለወንጀለኞች ቅንጣት ቀዳዳ በማይፈጥር መልኩ እንደገና መደራጀት አለበት» ብለዋል፡፡

ቻይና በምግብ ደህንነት ቁጥጥር ላይ የተለየ ትኩረት ማድረግ የጀመረችው በተለይ በ2008 በምግብ ውስጥ ባዕድ ነገር በማደባለቅ ምክንያት ከተፈጠረው የጤና ጉዳት ክስተት በኋላ ነው፡፡ ሳን-ሱ ግሩፕ የተባለው ታዋቂና ግዙፍ የሕፃናት ወተት አምራች ኩባንያ በወተቱ ውስጥ ሜላማይን (Melamine) የተባለ ጎጂ ኬሚካል ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት ለበሽታ ሲዳረጉ አራት ልጆች ደግሞ ሞተዋል፡፡ ይህ ሜላማይን የተባለ ኬሚካል ለፕላስቲክ መስሪያ ግብአት የሚውል እንጂ ምግብ ውስጥ የሚደባለቅ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሜላማይንን ወተት ውስጥ የቀየጡት ወተቱ በፕሮቲን የበለፀገ እንዲመስል ለማድረግ ነበር፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ባሳለፍነው ወር (Jan,2017) የቻይና የምግብ ደህንነትና የመድኃኒት አስተዳደር ባወጣው መግለጫ 35 የምግብ ሥራ (ካተሪንግ) ኩባንያዎች በምግብ ውስጥ ኦፒየም (Opium) የተባለ ሃሺሽ ደባልቀው መገኘታቸው ተረጋግጧል፡፡ ኦፒየም የተባለው ሀሺሽ ለምግብ ግብአትነት እንዳይውል ከረጅም ጊዜ በፊት የተከለከለ ቢሆንም በምግብ ዘርፍ ያሉ ወንጀለኞች ግን ዛሬም ድረስ ጨለማን ተገን አድርገው እየቀየጡት ይገኛሉ፡፡ ቻይናም ሆነች ሌሎች አገራት በከፍተኛ ደረጃ ካስቀመጧቸው አስር የደህንነት ጉዳዮች ውስጥ የምግብ ደህንነት ስጋት በአንደኛ ደረጃ የሚቀመጥ ችግር ነው፡፡ ቻይና የምግብ ደህንነት ጥበቃ አስተዳደር ሕጎቿን በ2015 አሻሽላ አጠናክራለች፡፡ በዚህ ሕግ መሻሻልና መጠናከርም ታላላቅ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡

የሕግ አስከባሪና አስፈፃሚ ቡድኖች በሰሩት የቁጥጥር ሥራ ከተለያዩ የምግብ ሠሪና አቅራቢ ኩባንያዎች የተወሰዱ ናሙናዎች 96ነጥብ8 በመቶ ያህል ተገቢውን መመዘኛ ያሟሉ ምግቦች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ ከተወሰዱ ናሙናዎች መካከል ማለት ነው እንጂ በአገሪቱ የሚገኙ ኩባንያዎችን ሁሉ የሚያጠቃልል አይደለም፡፡ አሁንም ድረስ የምግብ ደህንነት ጉዳይ ተቀዳሚ ትኩረትን የሚሻ ነው፡፡ ዋናው ችግር የሕጉ መላላት፣ የሕግ አስከባሪ ኃይሉ ብቃት ማነስ፣ የምግብ ደህንነት መመርመሪያ፣ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችና የሠራተኞች ክህሎት ዝቅተኛነት፣ እንዲሁም ለምግብ ደህንነት ብቻ የታሰቡና የተደራጁ የምርመራ ተቋማት (ኢንስቲትዩት) እንደልብ አለመገኘት… ናቸው፡፡ ተገቢ ካልሆኑ ነገሮች ጋር የተቀየጡና የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ (Adulterated) ምግቦችና፣ ሀሰተኛ የምግብ ዓይነቶች ለምሳሌ የታሸጉ የሩዝ ዓይነቶች በሕዝቡ በተለይም በሕፃናት ጤናና ሕይወት ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመከላከል ጠንካራ ሕግ በማውጣትና በብቃት በማስፈፀም ረገድ የመንግሥት ሚና ወሳኝ ነው፡፡

የእኛም አገር የምግብ ደህንነት አስተዳደርና ቁጥጥር ችግር ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ባዕድ ነገሮችን በጥሩ የምግብ ግብአቶች ውስጥ በመጨመር መጠኑ (ኪሎው) እንዲበዛና ጥራቱ እንዲጎድል የማድረግ (Food Adulteration) ወንጀል ዛሬ የተጀመረ አይደለም፡፡ ቅቤና ሞራ መቀየጥ፡ ማርና ስኳር መበጥበጥ፣ በርበሬና ቀይ አፈርን አብሮ መውቀጥ፣… ድሮም የነበረ ነው፡፡ አዲሱ የምግብ ደህንነት ስጋት ከእንጀራ ግብአቶች ጋር የሚቀየጠው ጀሶ የተባለው ነገር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ አረመኔ ያዊነት ነው፡፡ እንጀራ ሁሉም ሕዝብ የሚበላው ነው፡፡ ጥፋቱም በሁሉም ሰዎች ላይ የተሰራ ነው፡፡ በሰማይ ሀጢአት፣ በምድርም ወንጀል ነው፡፡ የሰማዩን ለጊዜው ትተን በምድራዊ ወንጀልነቱ ላይ መነጋገር አለብን፡፡ ሕጋችን በእነዚህ ወንጀለ ኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ምንድ ነው? ሊጥ መድፋት፣ ቡሃቃና መስቲውን መገልበጥ ባልዲ ውንና ምጣዱን መውረስ…ከዚያስ ? ጥፋተኛው ላይ ቀላል እስርና የጥቂት ብር ቅጣት መጣል ይበቃል!

የመድኃኒት ቁጥጥርና አስተዳደር ዘርፉንም ብንወስድ መሻሻል ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ የሀሰተኛ መድኃኒቶች ዝውውር ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡ ለምሳሌ ፋርማሲ ገብታችሁ የሆነ መድኃኒት ብትጠይቁ ፋርማሲስቱ መጀመሪያ የሚጠይቃችሁ «የየትኛውን አገር ነውየሚል ነው፡፡ የፈረንሳይ? የጀርመን? የሳይፕረስ ቆጵሮስ? የፈረንሳዩን ብትሉት ያ መድኃኒት የፈረንሳይ ስለመሆኑ ወይም በፈረንሳይ የተመረተ መሆኑን እንዴት ማረጋገጥ ትችላላሁ? ወረቀቱ ላይ (Made in France) የሚለውን ያሳያችኋል፡፡ ወረቀቱን አይታችሁ ማመን የለባችሁም ወይም አይገባችሁም፡፡ ምክንያቱም በየጉራንጉሩ የተሰሩ መድኃኒቶች የታላቅ አገሮችን ስምና አርማ በተመሳሳይ ሁኔታ አሰርተው (ሰርተው) ይለጥፋሉ፤ ባዶ የጠመኔ (ቾክ) መስሪያ ዱቄት በመድኃኒት ቅርጽ እየጠፈጠፉ የሚያሰራጩ ወስላቶች በየቦታው (በየአገሩ) አሉ፡፡ በዚህ ረገድ ከተቸገሩ አገሮች አንዷ ጣሊያን ነች የውሸት (Made in Italy ) የሚል የተለጠፈበት በስሟ እየሰሩ የመድኃኒት አምራችነት ክብሯን ጥቅሟንና ግጽታዋን በሚያጠፉ ሕገወጦች ተቸግራ ኖራለች፡፡ አሁን ግን ዘዴ አበጅታለች፡፡

የጣሊያን መድኃኒት የሆኑትንና ያልሆኑትን የሚለይ ሪሊያቢሊቲ (reliability) የተባለ አፕሊኬሽን (App) ሠርታለች፡፡ ይህ አፕሊኬሽን መድኃኒቱ ላይ ያለውን መለያ (ባርኮድ) ይወሰድና የጣሊያን ስለመሆኑና አለመሆኑ ማረጋገጫ ይሰጣችኋል፡፡ ሳትጠራጠሩ እንድትገዙና እንድትጠቀሙ ይረዳችኋል ማለት ነው፡፡ ስለ መድኃኒቱ አገልግሎትና ግብአት ዝርዝር መረጃ ያቀርብላችኋል፡፡ ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ባር ኮድ የመጠቀም ሕግ መኖር አለበት፡፡ ካለም መጠናከርና ተፈፃሚነቱ መረጋገጥ አለበት፡፡ ማንኛውም በፋርማሲና በሱፐር ማርኬት የሚደረደር ምግብም ሆነ መድኃኒት ባር ኮድ ሊኖረው ይገባል፡፡ በትክክል በተጠቀሰው በሀገር የተሰራ መሆኑን የሚያረጋግጥበት ቴክኖሎጂ/ አፕሊኬሽን ያስፈልገዋል፡፡ በሻጭና በገዢ መካከል መተማመን አልተቻለም፡፡ መንግሥትም (የምግብ ደህንነትና የመድኃኒት አስተዳደር ኤጀንሲ) በርካታ የተቆጣጣሪ ሠራዊት አሰማርቶ እግር በእግር መከታተሉ ቢቸግር ነው እንጂ ጥሩ ዘዴ አይደለም፡፡ ለሙስናም ያጋልጣል፡፡ የታሸገ ምግብና መድኃኒት በሙሉ በባር ኮድ ቢጠቀም ግን ችግሩ ይቃለላል፡፡ ተጨማሪ ሕግ የሚያስፈልገው የመፍትሔ ሃሳቦችን ፈር ለማስያዝና አፈፃፀሙን ተግባራዊ ለማድረግ ነው፡፡

 

ግርማ ለማ

 

 

Published in አጀንዳ

 

ኢትዮጵያና የሰላም ማስከበር ስራ የተዋወቁት በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት እንደሆነ፤ ኮሪያና ኮንጎም የመጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሰላም ለማስከበር የተጓዙባቸው አገራት ስለመሆናቸው ታሪክ ይነግረናል። የኢትዮጵያ ሰራዊት በእነዚህ አገራት ሰላም የማስከበር ተልእኮውን በአኩሪ ሁኔታ ስለመወጣቱም ዓለም የሚያውቀው እውነታ ነው።

ገና ማልዶ ለዓለም በተለይም ለአፍሪካዊያን ወንድም አገራት ሰላም ዘብ የመቆም የኢትዮጵያ ጅምር የተስተጓጎለው በወታደራዊው የደርግ መንግስት ነው። የደርግ መንግስት በባህሪው ከሰላማዊ መንገድ ይልቅ ሃይልና ጦርነትን ይመርጥ ስለነበረም እንኳንስ ለአፍሪካዊያን ይቅርና ለአገር ውስጥ የሚተርፍ ሰላምን ማረጋገጥ ተስኖት ዘመኑን ቋጭቷል። የደርግ ዘመነ መንግስት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የችግሮች ሁሉ ምንጭ የውጭ ተጽዕኖ ነው የሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ስለነበረው ከጎረቤት አገራት ጋር የነበረው ግንኙነትም የሻከረ ነበር።

የደፈረሰው የአገር ውስጥ ሰላም በውጪ ዓለምም የሚንጸባረቅ ነበረናም ኢትዮጵያ ቀደም ብላ የጀመረችው በአፍሪካ ሰላም የማስከበር ተልዕኮ ተገታ፤ ፍላጎት ነበረ ቢባልም እንኳን እንደ አገር ኢትዮጵያ ያንን ማድረግ የምትችልበት አቅምና አቋም ላይ አልተገኘችም።በዚህም ምክንያት ለ30 ዓመታት ያህል በሰላም ማስከበር ተልእኮ ላይ አልተሳተፈችም። ይህ ሁኔታ በ1983 ከተደረገው የመንግስትና የስርዓት ለውጥ በኋላ ዳግም ተመልሶ ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

በተለይም የችግሮች ሁሉ ምንጭ የውጭ ጫና ነው የሚለው የደርግ ፖሊሲ፤ የችግሮች ሁሉ ምንጭ የውስጥ ችግር ነው ወደሚል አቅጣጫ ከተለወጠ በኋላ ኢትዮጵያ የውስጥ ሰላሟን ፍፁም ማረጋገጠ ችላለች።ይህ ሰላሟ ደግሞ ለወንድም አፍሪካዊያን ተርፏል። ለመጀመሪያ ጊዜም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ቁጥር 40 መሠረት የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ሃይል በ1986 /ም በሩዋንዳ ተሰማርቶ የፀጥታና የደህንነት ሽፋን በመሥጠት ተልእኮውን በአስተማማኝ መንገድ ተወጣ፡፡ ቀጥሎም በብሩንዲ፣ በላይቤሪያ፣ በዳርፉር፣ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን አዋሳኝ ድንበርና በሶማሊያ ያበረከተውና እያበረከተ ያለው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እንኳንስ ወዳጅ አገራትን ጠላትንም ያስደመመ ሆኗል።

በአጠቃላይ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ውስጥ ከ35 ሺህ የሚልቅ የሰላም አስከባሪ ሰራዊት ግጭቶችና ውጥረቶች ወደተንሰራፉባቸው የአፍሪካ አገራት ልካለች። በዚህም የሚሊዮኖችን ሰላማዊ ዜጎች ህይወት መታደግ ችላለች፤ አገራቱንም ከቀውሶች ታድጋለች። ይህ ለአፍሪካ የነጻነት ቀንዲል ለሆነች አገር ትልቅ ኩራትም ብርታትም ነው።

የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተግባር የዓለም አገራትን እውቅና ያሰጠ ስለሆነም በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት ተለዋጭ አባል እንድትሆን አግዟታል። በአህጉር ደረጃም እአአ ከ2002 ጀምሮ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ካውንስል ውስጥ ለስምንት አመታት፤ እንዲሁም ከ2015 እስከ 2017ም ለሁለት ዓመታት አባል ሆና እንድታገለግል አስችሏታል፡፡ ይህ ተሞክሮ አሁን ወደ ላቀ ኃላፊነትና ተግባር ማደግ አለበት ተብሎ ይታመናል። ጊዜውም ነው።

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው 28ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ ከብዙዎቹ አጀንዳዎቹ መካከል አንዱ የሆነውን በህብረቱ ስር ለሚገኙ ኮሚሽኖች ኮሚሽነር ምርጫ አካሂዷል። የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽን ምርጫም አንዱ ነው። ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እያበረከተችው ካለው አስተዋጽኦ አንጻር፤ የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽን ኃላፊነት ቦታ አይመጥናት ይሆን? አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው ምሁራንና ባለሙያዎች ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ለዚህ ኃላፊነት አቅሙም፤ ብቃቱም እንዳላት አረጋግጠዋል።

ስለሆነም አሁን ወቅቱ ኢትዮጵያ ለዚህ ቦታ መመጠኗን የምታሳይበትና ኃላፊነቱን ተቀብላ በሰላም ማስከበር ዙሪያ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ የምትደግምበት ሊሆን ይገባል። ይህንን ቦታ ለማግኘት በኢትዮጵያ በኩል የተደረገ ጥረት ስለመኖሩ መረጃ የለም። ሆኖም ቦታው በውድድር የሚገኝ እንደመሆኑ ፉክክሩ ቀላል እንደማይሆን ምሁራኑ ገልጸዋል። ስለሆነም "ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም" እንዲሉ ከባዱ ፉክክር ተፈርቶ ከባዱን ኃላፊነት መተው ተገቢ አይሆንም።

ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት ከባድ ፉክክርና ቅስቀሳ አድርጋ ያሸነፈች አገር፤ ስለሰላሟና ደህንነቷ ብዙ በከፈለችላትና እየከፈለችላት ባለች አህጉር ውስጥ ለሚኖር ፉክክር ትረታለች ማለት ሳያጣሩ ወሬ ሳይገሉ ጎፈሬ ይሆናል ነገሩ። በመሆኑም መንግስት የአፍሪካ አገሮችን ይሁንታ ማግኘት፣ ለቦታው ብቁ ሰው ማዘጋጀት፣ በፈረንሳይኛ ተናጋሪና በእንግሊዘኛ ተናጋሪ አገራት መካከልም ያለውን ሹክቻ በዲፕሎማሲ ማርገብ ከቻለ ቦታውን መያዝና በሰላም ማስከበር ዙሪያ ያበረከተውን የላቀ አስተዋጽኦ በህብረቱ የሰላምና የደህንነት ኮሚሽን መሪነት ላይም ኃላፊነቱን በሚገባ በመወጣት መድገም ይችላል። ለዚህ ደግሞ ረጅም ጉዞ ይጠይቃልና፤ ጉዞው ከአሁኑ ይጀመር።

 

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።