Items filtered by date: Sunday, 05 February 2017

 

                           ፀደይ ፋንታሁንና ሙሉጌታ ዘሚካኤል የመጨረሻውን ውድድር ባደረጉበት ወቅት፤

 

በኢትዮጵያ የጥበብ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች ለማግኘት ችሎታ እና አቅማቸውን እንዲያሳዩ ምቹ ዕድል የመፍጠር አጋጣሚ ቀደም ባለው ጊዜ አናሳ ነው። እንዲያውም የሉም ማለት ይቻላል። ይሁንና ዛሬ ዛሬ ግን አንዳንድ ተከታታይ የተሰጥኦ ውድድር የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ተሰጧቸውን እንዲያሳዩ መድረኮችን ማመቻቸት እየተለመደ መጥቷል። ይህ ሲባል ግን አንድ ዘርፍ ለይቶ መሥራቱ ላይ ግን የተለመደ አልነበረም። ይህንን የተገነዘበው ቦጋስ ፕሮዳክሽን  «የማለዳ ኮከቦች» በሚል   የተዋናይነት ውድድር ብቻ ይዞ ተነስቷል።

«የማለዳ ኮከቦች» እየሠራ ያለው  በአገር ደረጃ ብቸኛ ነው ብንል ስህተት አይሆንም። ምክንያቱም ሌሎቹን ስንመለከት የተለያየ ተሰጦ ያላቸውን ሰዎች ነው የሚያወዳድሩት።  ይህ ሲባል ግን የእነርሱ ሥራ ውስንነት አለበት ለማለት እንዳልሆነ ተደርጎ ይወሰድ። ዝንባሌ ያላቸውን ወጣቶች በየትኛው ዘርፍ መሰማራትና መሥራት እንደሚችሉ በማመላከት ደረጃ የጎላ ሚና ይኖረዋል። ነገር ግን አንድን ዘርፍ መርጦ ማወዳደሩ  የበለጠ በዘርፉ   ብቃት ያለው ባለሙያ ለማፍራት እገዛ ይኖረዋል። ተወዳዳሪው እየተማረ በመሄድም ለቀጣይ ብቃቱን አሻሽሎ እንዲመጣም ያግዘዋል።

«ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉንም ማለት ባይቻልም ብዙኃኑ የትወና ጥበብ ያለው ነው። ይህንንም የተመለከትኩት ለውድድርና ለስልጠና ወደ ተቋማችን የሚመጣውን ስመለከት ነው። አዛውንት፣ሕፃናት፣ ወጣት  ጎልማሳ አገሪቱ ውስጥ ምንም የቀረ ሰው የሌለ እስኪመስለኝ ድረስ በምዝገባ እራሴን ያጨናነኩበትን ወቅት እንዲህ በቀላሉ የምገልጸው አይደለም» የሚሉት በቦጋስ ፕሮዳክሽን የማለዳ ኮከቦች ማሰልጠኛ ተቋም ርዕሰ መምህር ወይዘሮ ቦጋለች አደፍርስ ናቸው። 

እርሳቸው እንደሚሉት፤ አሁን እየተከናወነ ባለው ውድድር ተሰጦውን የሚያሳዩበት መድረክ ሲያገኙ ምን ያህል ብቃት እንዳላቸው ከባለሙያው አልፎ ማህበረሰቡ እንኳን ዳኝነቱን ሲሰጥ ይስተዋላል። ስለዚህ እንደነዚህ ዓይነት መድረኮች ተዋናዮችን ለማፍራት ብቻ ሳይሆን ማን በምን ዘርፍ ላይ መሰማራት እንደሚችልም የሚያመላክቱ ናቸው። ለሥራ ዕድልም ቢሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል። በዚህ መድርክ የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራሙ ከሥነምግባር አንስቶ እስከ ማህበረሰቡ ችግሮች ድረስ የሚቃኝበት ነው።  የችግር መፍቻ መሳሪያዎችን እንዲሁ በማመላከት በስፋት የተሳሰረ ዝግጅት ይቀርብበታል። በመሆኑም ይህ ዘርፍ ሊጠናከር ይገበዋል።  

በብዙ ውጣውረድ ውስጥ አልፎ አሁን ብዙዎችን የዘመኑ ፈርጦች እያደረገ ያለውን «የማለዳ ኮከቦች» የቴሌቪዥን የተሰጥኦ ውድድር በተመለከተ በተለያየ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል እያፈራ ነው ሲሉ የነገሩን ደግሞ በቦጋስ ፊልም ፕሮዳክሽን «የማለዳ ኮከቦች» የፕሮዳክሽን ማናጀር አቶ እስከዳር አስፋው ናቸው። ብቃት ያለው የሰው ኃይል እንዲፈራ በትምህርት ዘርፍ የትምህርትና ቴክኖሎጂ ሠራዊትን መገንባት ይገባልም ይላሉ።

«ትወና እንዲሁ የተሰጠን መክሊት ብቻ በመያዝ የሚዳብር አይደለም» የሚሉት አቶ እስክንድር፤   በትምህርት መታገዝ እንዳለበት ያሳስባሉ። ሆኖም በአገር ደረጃ ይህ እየተደረገ አለመሆኑ አዘጋጆች የፈለጋቸውን ሰው ከመንገድ ላይ እየወሰዱ ሲያሠለጥኑ ይስተዋላል። ይህ ደግሞ ለፊልም ኢንዱስትሪው መበልጸግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይፈጥራል። ይሁንና እስከአሁን ባለው ሂደት ይህንን ዘርፍ ለማሳደግ እየተደረገ ያለው ጉዞ ብዙም አልነበረም። ስለዚህ ይህንን ዘርፍ ለማጠናከርና በርከት ያሉ ተዋናዮችን በሙያው የተካኑ አድርጎ ለማፍራት የማለዳ ኮከቦች ሥራውን አጠናክሮ እየቀጠለ እንደሆነ ነግረውናል።

እንደ አቶ እስክንድር ገለጻ፣ ተዋናዮችን በአግባቡ አሠልጥኖ ማውጣት ለፊልም ዳይሬክተሮችም ሆነ ለአዘጋጆች እንዲሁም ፊልሙን ለሚያየው ማህበረሰብ እጅግ የላቀ ሚና ይኖረዋል። በተለያየ ደረጃ ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎችም ቢሆን ጠቃሚ ነው። በተለይ ለፊልም ኢንዱስትሪው የሚያበረክተው አስተዋፅኦ እንዲህ በቀላል የሚገለጽ አይደለም። ይሁን እንጂ ይህ ዘርፍ ጠንካራ እንዲሆን በየደረጃው ያሉ የትምህርት ባለሙያዎችና አርቲስቶች፣ የመንግሥት ድጋፍና የማህበረሰቡ ተሳትፎ ያስፈልጋል።

በአሁኑ ወቅት ተቋሙ የፊልም ተዋናዮች ማከፋፈያ ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ነው። ይህ ደግሞ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር ተሰጦ ያላቸውን ሰዎች አቅማቸውን እንዲለዩ ያደርጋቸዋል። በተለያየ የፊልም ሥራ ላይ ተግባራትን እያከናወኑ ያሉ አካላትንም ብዙ ሳይቸገሩ ሥራቸውን በፍጥነትና በጥራት እንዲያጠናቅቁ ያግዛቸዋል። ይህንን ደግሞ በተለያዩ መድረኮችና በሚሰጡን አስተያየቶች ለማረጋገጥ እንደቻሉም ነበር የገለጹልን። ይበልጥ ለአርአያነት የሚያበቃ ሥራና ተግባር የፈፀሙ የዘርፉ ተዋናዮችን መሸለምና እውቅና መስጠታቸውም ለበለጠ ሥራ እንደሚያነሳሳቸው ተቋሙ ያምናል። በዚህም ከዚህ ተቋም ሽልማት ወይም እውቅና የተቸራቸው ተዋናዮች በየመድረኩ የዚህ ተቋም ፍሬዎች እንደሆኑ እየገለጹ ነው። አጋሮቻቸውም በዚህ ተቋም ነጥረው በመውጣ ታቸው ሳያስቸግሯቸው መሥራት እንደቻሉ በተለያየ አጋጣሚ ይናገራሉ። ስለዚህ ይህ ተቋም ተሰጥኦ ያላቸውን ተዋናዮች በማፍራት ተግባሩ የተሳካለት እየሆነ ነው ቢባል ድፍረት አይሆንም ባይ ናቸው።

«የአንድ ቤተሰብ ፍንካቾች፣ የ«እናት ሆድ ዥንጉርጉር» የሚለውን አባባል ማሳያዎች፣ የዘመኑ ወጣት ምሳሌዎች የሆኑ ዜጎች በብዛት ሲሳተፉ የምናይበት ይህ ፕሮግራም ብዙዎችን አስፈንጥዟል» የምትለው  የመጀመሪያው ዙር ተወዳዳሪና ከሴቶች ቡድን ውስጥ የአንደኝነት ደረጃን በመያዝ ተሸላሚ የነበረችው ተዋናይት ጸደይ ፋንታሁን ናት። ጸደይ ምንም እንኳን ከደብረዘይት ድረስ እየተመላለሰች ይህንን የትወና ውድድር ብትሳተፍም ዓላማዋ ማሸነፍ ስለነበር ከብዙ ውጣውረድ በኋላ  ካሰበችው ደረጃ ላይ መድረሷን ትናገራለች።

 ዛሬ ላይ አንገት ደፊና ጫማ ሠፊው አባቷ የሚንሰፈሰፉላት ኮረዳ በመሆን በዘመን ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ መተወኗን ቀጥላለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ብዙዎቹ ተወዳዳሪዎች በተለያዩ የፊልምና የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማ እንዲሁም የመድረክ ድራማ ላይ እየተሳተፉ ናቸው የምትለው ጸደይ፤ ይህ ሊሆን የቻለው ብቃታቸው በዚሁ የመድረክ ትወና ላይ እንዲፈተሽ በመደረጉ እንደሆነ ታስረዳለች።

«የማለዳ ኮከቦች» ላይ የመሳተፍ ዕድል ያገኘችው የቴሌቪዥን ማስታወቂያ መመልከት በመቻሏ ነበር። ከዚያም ውድድሩ ላይ ከተሳተፉት 1050ተወዳዳሪዎች መካከል አንዷ መሆን እንደቻለች ትገልጻለች። ጸደይ ከአንድም ሁለቴ የምልመላ ፈተና ወስዳለች። በዚህም15ቹ ውስጥ ለመቀላቀል በሚደረገው ፈተና ማለፍ ሳትችል እንደቀረች አውግታናለች። ሆኖም  በነበሩት ፈተናዎች ሳትበገር ነጥራ በመውጣቷ ሙያውን የበለጠ እንድትወደው ሆናለች። ዛሬ በዘመን ድራማ ላለችበት የተዋናይነት ብቃት የደረሰችውም ሌላ ዕድል በመመቻቸቱ እንደሆነ ነው የነገረችን። ስለዚህም ውድድር እና ፈተና  አዲስ ነገሮች እንዳልሆኑ ገልጻልናለች።

 «ተዋኝ ለመሆን ማሰብ የጀመርኩት ገና በዘጠኝ ዓመቴ  ነበር» የምትለው ጸደይ፤  ይህ ውድድር ህልሟን ለማሳካት ላደረገችው ጉዞ መንገዱን እንደጠረገላት ታስረዳለች። ዛሬም ሆነ ነገ ባለችበት ዕድሜ ውስጥም ብዙ ፈተናዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ታምናለች። ስለሆነም ማንኛውም ለትወና የሚወዳደር ሰው በፈተና ውስጥ ሲያልፍ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለበትም ነው የምታስገ ነዝበው።

 ውድድሩ ሦስተኛ ዙር ደርሷል። እርሱ ግን የመጀመሪያዎቹ የማለዳ ኮከቦች ምርጥ ነው። አንደኝነትንም  በመያዝ ነበር ውድድሩን ያጠና ቀቀው። ዛሬ ላይ ደግሞ «ዘመን» ድራማ ላይ ምርጥ ከያኒ በመሆን እየተሳተፈ ይገኛል። ሌላው ያነጋገርነው ተዋናይ ሙሉጌታ ዘሚካኤል።

ሙልጌታ «ሁል ጊዜ ተዋናይ መሆንን እመኛለሁ። ሆኖም በተለያዩ ደረጃዎች ብሳተፍም ስኬታማ ግን አልነበርኩም። እንዲያውም በሬዲዮ አጫጭር ድራማዎች ውስጥ እሠራ ነበር። በእርግጥ በሙያው ተምሬ ተመርቄበታለሁ። ይሁንና የሥራ አማራጩ ብዙም አይደለምና ሌላ ሥራ መሥራት እንዳለብኝ አምን ጀመር። ብዙ ጊዜ እሳተፋለሁ በዚያው ልክ ግን ተስፋ እቆርጥ ነበር» ይላል። ከብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ ግን በማለዳ ኮከቦች ላይ ተሳተፈ። በየጊዜው አዳዲስ የትወና ጥበቦችን እየተማረ መጣ።

 ገንዘብ ለማግኘት አለ የተባለውን አቋራጭ መንገድ ሁሉ የሚያስስ እንደነበር የሚናገረው ሙሉጌታ፤  የትወና ብቃት ቢኖረውም  በየትኛው መድረክና በየትኛው መምህር መማር እንደሚችል ባለማወቁ እራሱን ሸሽጎ ነበር።  የማለዳ ኮከቦች  መምህራን ማንነቱን እንዲያይ እንዳደረጉትም አውግቶናል። በዚህም ኮከቦችን የማፍራት ጅማሮ በቴሌቪዥን መስኮት ላይ ብቅ ሲል እርሱም አብሮ ብቅ ማለቱን ጀምሯል። ስኬታማም ሆኖበታል። በእርግጥ ወደ ውድድሩ ሲገባ በአጋጣሚ ነበር፡፡ እንደያውም ውድድሩን እየተሳተፈ እያለ የተመዘገቡትንና በመሥራት ላይ ያሉትን ሰዎች ሲመለከት እርሱ ምንም እንዳልሆነ ተረዳ። በዚህም መጀመሪያ የነበረው ተስፋ መቁረጥ ዳግም እንደተመለሰበት ያስታውሳል።

ከዚያም ወደ ቤቱ ሄዶ እንዳልተሳካለት በማመን ሌሎች አማራጮችን ማፈላለጉን ቀጠለ። ከሳምንታት በኋላ የተሻለ ሥራ ያከናወኑት ተወዳዳሪዎች ስም ተለጠፈ። እርሱ ግን አልፋለሁ ብሎ ስላልገመተ አላየም። ከእርሱ ጋር አብሮት የተመዘገበ ጓደኛው ማለፉን ያበስረዋል። በዚህም በድጋሚ ተስፋው ለምልሞለት  ወደ ሥራው ገባ። ይህ ቀላል አጋጣሚ ወደ ጥበቡ ዓለም ጎትቶ ማምጣት ብቻ ሳይሆን በሙሉ ጊዜ ትያትር ላይ ለመተወን ዕድሉን ከፈተለት፡፡ ውድድሩ ሁለተኛ የትወና ትምህርት ቤቱም ሆነ። ስም ካላቸው ተዋንያን ጎን መሰለፍም ቻለ። ታዲያ እርሱም እንዳለው፤ በፊት ከተማርኩት በላይ በማለዳ ኮከቦች ውድድር የተማርኩት ይልቃል። በመሆኑም ይህ ተዋናይን የማፍራቱ ጅማሬ ጠንክሮ ይሠራበት ሲል ያሳስባል።

ይህ ተዋናይን የማፍራት እንቅስቃሴ ምንም እንኳን መቀመጫውን አዲስ አበባ ቢያደርግም በየክልሉ እየተዘዋወረ ተሰጥኦ ያላቸውን ሰዎች ማፈላለጉን አላቋረጠም። ሥራ አጡን፣ ከስደት ተመላሹን፣ ተማሪውና አስተማሪውን፣ ባለትዳሩንና ላጤውን፣ እናትና ልጅንና ሌሎችንም በማሳተፍ እርስ በእርስ ሲፋተጉ ያሳየናል፡፡ ይህንን ውድድር ለመሳተፍ ብዙዎች ይፈልጋሉ። ሆኖም ከአንዴ በላይ በሚደረገው ጉዞ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት መሳተፍ ይከብዳቸዋል። ለዚህም ደግሞ አዘጋጆቹ ይህንን ችግር የሚፈታ መፍትሔ አስቀምጠዋል። ይኸውም «በሽታውን የደበቀ መድሃኒት አይገኝ ለትም» እንዲሉ ዓይነት ነው። ችግሩን የተናገረ በውድድሩ የሚሳተፍበትን አማራጭ ይዘጋጅለታል። ለዚህም ደግሞ በማሳያነት የምትጠቀሰው ቤተልሄም ኢሳያስ ነች።

ቤተልሄም በጎንደር አካባቢ ገጠራማው ክፍል ነው የምትኖረው። ከአያቷ ጋር ስለሆነችም እየተመላለሰች ውድድሩን እንድታደርግ የሚችሉበት ገንዘብ የላቸውም። እርሷ ግን ተሰጥኦ ያላት ልጅ ናት። እናም ይህንን ችግሯን ለአዘጋጁና የማለዳ ኮከቦችን ላቋቋመው ፍጹም አስፋው ነገረችው። እርሱም በቅርብ ርቀት የምትማርበትንና የምትወ ዳደርበትን ምቹ ሁኔታ ፈጠረላት። በቴአትር ዓይኗን እንድትገልጥም አደረጋት።

በአንድ ቴአትርና ፊልም ተሳትፎው ዕውቅና እና ተከታታይ ሥራዎች እንደሚመጡ የምታምነው ቤተልሄም፤ በማለዳ ኮከቦች በሁለተኛው ዙር ከሴቶች አንደኛ በመውጣት ተሸልማለች። ባገኘችው የተዋናኞች ምልመላ ፈተና ላይ ብቃቷን አሳይታ ለችም። ዛሬም ቢሆን እንዲሁ ከትምህርቷ ጎን ለጎን በዘመን ፊልም ላይ የገጠሯን ሙስሊም ሴት  «መታሰቢያ» የተሰኘችውን ገጸ ባህሪ በመላበስ እየሠራች ነው። በእርግጥ «ሳይደግስ አይጣላ» አይደል የሚሉት አበው እርሷን ከጎንደር አምጥቶ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ አድርጓታል። ይህ ደግሞ በቅርብ ሆና መምህራኑ የሚሰጡትን ትምህርት እንድትከታተል አግዟታል።

 በቅርቡ አንደኛና ሁለተኛ ዙር ተወዳዳሪዎችን በጥምረት በማድረግ እየተሠራ ላለው የፊልም ሥራም ዕጩ ስለሆነች በአግባቡ እንድትሠራበት እየረዳት እንደሆነ ነግራናለች። በምትተውናቸው ፊልሞች ላይም ፈተና ሳይበዛባት በአግባቡ እንድትሠራ እያደረጋት እንደሆነም እንዲሁ ገልጻልናለች። ሩቅ ሳትሄድ የምትፈልገውን ሙያ እንድትተገብርም ሆናለች።

ቤተልሔም፤ ቀደም ሲል ስትመኘውና ስታደንቀው የቆየችውን «የሰው ለሰው» የቴሌቪዥን ድራማ ተወዳጅና ዝነኛ ተዋናይ አበበ ባልቻን አይታ፣ ከእርሱም ጋር መሥራቷ እንዳስደሰታት ትናገራለች። ይህ የሆነውም የማለዳ ኮከብ ኮትኩቶ በማሳደጉ እንደሆነ ትገልጻለች። እንደውም ውድድሩ አልቋል ስትባል ሁሉ ከእንደገና ሌላ ውድድር ላይ ልሳተፍ መዝግቡኝ የሚል ጥያቄ እንዳቀረበችም ታስታውሳለች። ይህንን ያደረገችው ለሚሰጣቸው ስልጠና ያላት ፍላጎት ላቅ ያለ ከመሆኑ የተነሳ እንደሆነ ነግራናለች።

ሌላው በአጋጣሚ ያገኘነውና ለውድድር ከደሴ ከተማ ደላልታ ወረዳ ለመመዝገብ እንደመጣ የነገረን  ሲሳይ መንግሥቱ ነው። እርሱ እንደሚለው፤ የማለዳ ኮከቦች ቴሌቪዥን ባለባቸው አካባቢዎች ሁሉ ይታያል። ተግባሩ ደግሞ ተሰጥኦ ያላቸውን ተዋናዮች ብቻ ማፍራት ነው። በተለይ ተሰጥኦአ ቸውን ለማያውቁ ሰዎች ሠፊ ዕድልን እየሰጠ ያለ ፕሮግራም ነው። ብዙዎችንም ማንነታቸውን እንዲረዱ እያደረገ ይገኛል። «ለዚህም ነው እንደኔ ዓይነት ወጣቶች ከርቀት ድረስ መጥተው ለመመዝገብ ፍላጎታቸውን የሚያሳዩት» ይላል።

«መተወን እወዳለሁ። ነገር ግን በአቅራቢያዬ ይህንን ተግባር የምከውንበት መድረክ ስለሌለ ወደዚህ መምጣት ግድ ሆኖብኛል። መጀመሪያ ላይ ትምህርት ቤት፣ ከዚያም ዩኒቨርሲቲ በትወናው ዓለም ውስጥ እሳተፍ ነበር። ይሁንና በትምህርት የተቃኘና በአሰልጣኞች የማገኘው በቂ እውቀት አልነበረም። ማለዳ ኮከቦች ላይ ግን ይህ አይከሰትም። ምክንያቱም በዳኞች አማካኝነት ምን ያህል ተገርተው እንደሚወጡ ቴሌቪዥን ላይ ሲቀርቡ እየተመለከትን ነው» ሲልም አስተያየቱን ለግሶናል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበባት ኮሌጅ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ መዝናኛ ላይ የሚያተኩሩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቁጥር ከፍ ማለትን ተከትሎ የተከታታይ ድራማዎች ቁጥርም እንዲሁ እየጨመረ መምጣቱ እሙን ነው። ይህ ደግሞ ፉክክሩን እንዲጠነክር  ያደርገዋል። ስለሆነም ይህንን ፉክክር ድል ለማድረግ የሚያስችለው በእንደዚህ ዓይነት ተግባራት ነጥረው የወጡትን ተወዳዳሪዎች ሲይዝ ነው። በእርግጥ ዩኒቨርሲቲዎችም እንዲህ ዓይነት ተግባራት ያከናውናሉ። ይሁንና በእንዲህ ዓይነት የቴሌቪዥን ውድድር መደገፉ ይበልጥ በተውኔቱ ዓለም የበቃ ባለሙያን ለማፍራት ያስችላል።

በትምህርቱ ብዙም ያልሄዱበትንም ቢሆን ተሰጧቸውን እንዲረዱበትም ያደርጋል። ምክንያቱም በትምህርት ደረጃ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያሉ ውድድሮች የሚከናወኑት ያልተማረውንም እስከማሳተፍ ይደርሳሉ።  ስለዚህም እንደ ማለዳ ኮከቦች ዓይነት የቴሌቪዥን ውድድር ለፊልም ኢንዱስትሪው  የጎላ ፋይዳ ይኖራቸዋል።

ለዚህ ደግሞ «ዘመን» የተሰኘውን  የቴሌ ቪዥን ድራማ እንኳን ብናነሳ እንዲህ በዩኒቨ ርሲቲም ሆነ በእንዲህ ዓይነት ውድድር ነጥረው የወጡ ባለሙያዎች እንዱሁም ወጣቶች በመሳተ ፋቸው ቀልብ እንዲስብ አድርጎታል ይላሉ። እነዚህ ወጣቶች ገጸ - ባህሪያቸውን ለመረዳት የሚያደ ርጉትን ጥረት እንብዛም የሚያደክም አይሆንም። በሥነ-ምግባርም ቢሆን እንዲሁ የተሻሉ ናቸው። አዘጋጆች ብዙ መግራት አይጠበቅባ ቸውም።  የረጅም ዓመታት የትወና ልምድ ካላቸው ተዋናዮች ጎን መሥራታቸውም እንዲሁ ብዙ ያስተምራቸዋል ነው ያሉት።

ዘርፉ ብዙ መታገዝ እንደሚገባው የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፤ ተዋናይ ለመሆን የሚመጣው ተወዳዳሪ በትንሹ መርካትን ስለሚፈልግም አስተያየት ሲሰጠው ቶሎ ይበረግጋል፤ ተስፋም ይቆርጣል። ስለዚህ የሚመለከተው አካል ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሊቸረው እንደሚገባ ያስረዳሉ። ተወዳዳሪዎቹ እንዲህ እንደአሁኑ የዝና እርካብን ከመርገጣቸው በፊት በርካታ ተስፋ አስቆራጭ ፈተናዎችም ይገጥሟቸዋል። የመተወን ፍላጎታቸው በቤተሰብም ሆነ በጓደኛቸው ላይወደድላቸውም ይችላል። በተለይ የሁሉም ፍላጎት ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ የሚጎተጉት ይሆንባቸዋል። ስለዚህ በዚህ ዘርፍ መወዳደርንም ሆነ መሳተፍን አይፈልጉም። ይሁንና በትዕግስት መወጣት ከቻሉ ችሎታቸውን ይበልጥ የሚያመቻቹበት ዕድልን ይፈጥርላቸዋል። ህልማቸውን ለመኖር መንገዱን ይጠርግላቸዋል ነው ያሉት።

 በተመሳሳይ ለተወዳዳሪዎች የሚሰጡ አስተያየቶች እነርሱን በሚመጥን ደረጃ ሊሆንም ይገባል ባይ ናቸው። ምክንያቱም ተወዳዳሪዎቹ በአካልም ሆነ በአመለካከት ያደጉ ላይሆኑ ስለሚችሉ አሠልጣኞችም ሆኑ ዳኞች ከኩፈሳም ሆነ የወረደ አስተያየት ከመስጠት ሊቆጠቡ እንደሚገባም ይናገራሉ።

 ስንቶች ከአባቶቻቸው እግር ስር ቁጭ ብለው መማር ችለዋል። ስንቶችስ በተሰጣቸው ነፃነት ተጠቅመዋል ሲባል መልሱን ለአንባቢው መተው ያሻል። ይሁንና ይህ መድረክ መፈጠሩ ብዙዎችን ተደናቂና ተዋቂ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። በተቋሙ እስከአሁን እውቅና የተሰጣቸው ምርጥ ተዋናዮች 72 ሲሆኑ፣ ከአጠቃላይ ተወዳዳሪዎች ውስጥ ከወንዱም ሆነ ከሴት ተወዳዳሪዎች ውስጥ ከአንድ እስከ ሦስት ለወጡት የገንዘብና የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ከተሸላሚዎቹ መካከልም ብዙዎቹ በክልል ደረጃ ያሉ  እንደሆኑም ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። አሁን ላይ እንደ ኮሌጅ በመሆን እያገለገለ ይገኛል። ጅማሮው ይጠናከር እያልን ለዛሬ የያዝነውን መጣጥፍ በዚህ እንቋጭ።

 

ጽጌረዳ ጫንያለው

Published in መዝናኛ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሀገሪቱን እግር ኳስ ስፖርት በማሳደግ እና በማስፋፋት በኩል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ቀደም ሲል በርካታ ተጫዋቾችን ለተለያዩ ክለቦች እና ለብሄራዊ ቡድን ሲመግብ የነበረው ፌዴሬሽኑ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን ለራሱ እንኳ ሳይበቃ የክልሎች እጅን እየጠበቀ በተተኪ ማፍራት ላይ መጠነኛ የሆኑ ድክመቶች እንደታዩበት ተጠቆመ፡፡

ፌዴሬሽኑ ትናንት የ2008ዓ.ም መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን አድርጓል፡፡ጥር 27ቀን 2009ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው ቸርችል ሆቴል በተካሄደው የ2008ዓ.ም ጠቅላላ ጉባዔው ላይ የተገኙ የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት የፌዴሬሽኑን የ2008ዓ.ም የስራ አፈጻጸም፣ የኦዲት ሪፖርቱን እና የ2009ዓ.ም የስራ እቅዱን በተመለከተ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡ በቀረበላቸው ሀሳብም ላይ ያሉትን ደካማ ጎኖች አመላክተው የእርምት እርምጃ እንዲወሰድባቸውም ጠይቀዋል፡፡

 የጠቅላላ ጉባዔው የመጀመሪያ አጀንዳ በሆነው የኦዲት ሪፖርት ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ ቀደም ሲል በፌዴሬሽኑ አቃቤ ንዋይ ሲቀርብ የነበረው የኦዲት ሪፖርት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በውጭ ኦዲተሮች ተጣርቶ መቅረቡ በመልካም ጎኑ ቢነሳም ያሳያቸው ግኝቶች ግን አነጋጋሪ ሆነዋል፡፡ በቀረበው ኦዲት ላይ ፌዴሬሽኑ በርካታ ክፍያዎችን ሲፈጽም የፋይናንስ ህጉን ባልተከተለ መልኩ መሆኑ ለተጠያቂነት እንደሚያበቃው በኦዲት ባለሙያው ይፋ ሆኗል፡፡በሪፖርቱ ላይ የፌዴሬሽኑ አብዛኛው የክፍያ አፈጻጸሙ የፋይናንስ ህጉን ያልተከተለ መሆኑን በክፍተት ተቀብሎ ለዚህ ችግር ፈጣሪ የሆነውን አካል በማጣራት ተጠያቂ እንዲያደርግ ባለ ድርሻ አካላቱ አሳስበዋል፡፡

የእለቱ ጠቅላላ ጉባዔ በሁለተኛ አጀንዳው ከያዛቸው ጉዳዮች ውስጥ የ2008ዓ.ም የስራ አፈጻጸም ሪፖርትን መስማት ነበር፡፡ ሪፖርቱን ያቀረቡት የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ገብረማርያም ናቸው፡፡ በሪፖርታቸው ላይ ፌዴሬሽኑ ባለፈው ዓመት ከ2 ሺ በላይ ጨዋታዎችን ማካሄዱን፣ በእነዚህ ጨዋታዎች ላይ 91 ያህል ቡድኖች ተሳታፊ መሆናቸውን፣ ለሴቶች እና ለተተኪ ተጨዋቾች ሰፊ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀሳቸውን፣ ውድድሮቹን ያለምንም ቅሬታ ለመምራት የአቅማ ቸውን ያህል መንቀሳቀሳቸውን አመላክተዋል፡፡

የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሪፖርተር በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ከታደሙ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች መካከል ይጠቀሳል፡፡ የጠቅላላ ጉባዔውን ይዘት እና የተነሱ ችግሮችን በተመለከተ ከፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ገብረማርያም እና ከፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት ትረፉ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

 ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ጌታቸው ገብረማርያም ቀደም ሲል ፌዴሬሽናቸው ባለበት የገቢ እጥረት በወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ስር በጥገኝነት ይተዳደር እንደነበር ጠቅሰው፣ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ግን ባደረጓቸው ርብርቦች ከሚያዘጋ ጇቸው ውድድሮች በሚገኘው ገቢ እና ስፖንሰር በማፈላለግ በፋይናንስ ራሳቸውን ችለው ለመውጣት ከጫፍ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

 ቀደም ሲል በወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ፋይናንስ ባለሙያዎች እና በፌዴሬሽኑ አቃቤ ንዋይ ሲመረመር የነበረው የፋይናንስ እንቅስቃሴያቸው በውጭ ኦዲተር መጣራት መጀመሩ በጎ ጅማሬ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ ይህን ያህል ጉድለት መታየቱን ግን በዝምታ እንደማያልፉት ቃል ገብተዋል፡፡ « በውጭ ኦዲተሮቹ የተገኘው ክፍተት ትክክል ነው፡፡ የተፈጠረው ግን በአቅም ማነስ ወይም በአሰራር ብልሹነት አይመስለኝም፡፡ ሆኖም ግን የተገኘው ጉድለት በግለሰብ ይሁን በድርጅት አጣርተን ተጠያቂ ማድረግ ላይ ግን አንደራደርም» ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ጌታቸው፤ ከኦዲት ሪፖርቱ ጋር በተያያዘ የደረሱበትን ውጤትም በቀጣዩ ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚያቀርቡ ቃል ገብተዋል፡፡

ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለውለታ የሆነው አዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተዳክሟል መባሉን እንደማይቀበሉት የተናገሩት አቶ ጌታቸው፤ቀደም ሲል በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ ለህይወታቸው አስጊ በሆነ ሁኔታ እግር ኳስን ለሚጫወቱ እግር ኳስ አፍቃሪያን በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ችግሩ ተቀርፎ በርካታ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለማስፋፋት እቅድ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡ « ከአዲስ አበባ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ጋር ተነጋግረን የራሳችንን ህንጻ ለመገንባት እና የመጫወቻ ሜዳም ለማሰራት ከስምምነት ላይ ደርሰናል» ያሉት አቶ ጌታቸው፤ በቅርቡም በየክፍለ ከተማው እና በየትምህርት ቤቶች በርካታ ተተኪ ተጫዋቾችን የማፍራት ስራው በትጋት እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

 « በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሴት እግር ኳስ ቡድኖች መመናመን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል» ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት ትርፉ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል የተቋቋሙ ቡድኖችም ሲፈርሱ እንደሚስተዋል የገለጹት ኃላፊው፣ከዚህ ዓመት ጀምሮ ግን የመፍረስ አደጋ የተጋረጠባቸውን የማጠናከር የፈረሱትንም በመደገፍ መልሶ የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሴት ቡድኖችን ለማጠናከር በሚል ከራማ ኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር ሴቶች ብቻ የሚሳተፉባቸው የእግር ኳስ ውድድሮች ለማዘጋጀትም ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ በእነዚህ ውድድሮች ላይ ከአስር የማያንሱ የሴት ቡድኖች ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ እንደሚሳተፉም አቶ ዳዊት በተለይ ለአዲስ ዘመን ተናግረዋል፡፡

« በፊት ብዙ ቡድኖች በስሜት ይመዘገቡ ነበር፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ዓመት 91 ቡድኖችን ነው ያወዳደርነው፡፡ በዚህ ዓመት ግን ከብዛት ይልቅ ጥራት ላይ አተኩረን 48 ቡድኖችን ብቻ ነው የመዘገብነው፡፡ ይህ ደግሞ በየጊዜው የመፍረስ አደጋ ላይ የሚጋረጡ ቡድኖችን ቁጥር ይቀንሳል» የሚሉት ኃላፊው፤ አቶ ዳዊት ቡድኖች ለመመዝገብ የግዴታ የመለመማመጃ ሜዳ፣ አሰልጣኝ እና ቢሮ ብሎም የቦርድ አባላት መኖር አለመኖራቸውን እንደሚያ ጣሩም ተናግረዋል፡፡ በየውድድሮቹ ላይ የእድሜ ተገቢነት ትልቁ ችግር መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተሰራበት ያለው የኤም አር አይ ምርመራ እንኳ ትክክለኛ ውጤት እንደማያሳይ ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም ፌዴሬሽናቸው ከእድሜ ተገቢነት ጋር ክፍተት እንዳይፈጠር ፌዴሬሽኑ ባሉት ሁለት የህክምና ባለሙያዎች ታግዞ የተሻለ ማጣራት እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል፡፡ በየውድድሩ ላይ የሚመጡ ክለቦችን ብቻ ማወዳደር የፌዴሬሽኑ ግብ እንዳልሆነ አቶ ዳዊት ገልጸዋል፡፡  

     የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለ2009ዓ.ም የ20 ሚሊዮን ብር በጀት አጽድቋል፡፡ ከዚህ በጀት ውስጥ 12 ሚሊዮን ብር ያህሉን አዲስ ለማስገንባት ላሰበው ህንጻ እንዲውል በጠቅላላ ጉባዔው ጸድቋል፡፡ ፌዴሬሽኑ ያሰበው ተሳክቶለት ህንጻውን ማስገንባቱ እውን ከሆነ ከሙያዊ እና ከበጀት ጥገኝነት ብቻ ሳይሆን ከቤት ጥገኝነትም ተላቆ የራሱ ህንጻ ይኖረዋል፡፡

 

ታምራት አበራ

Published in ስፖርት

 

ባለፈው ዓመት ጠቅላላ ጉባዔውን ያደረገው የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን ለመጪው አራት ዓመት ፌዴሬሽኑን በሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩ አዳዲስ አባላትን መርጧል፡፡ በጠቅላላ ጉባዔው አባላት ከፍተኛ ድምጽ አግኝተው ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ የተመረጡት የፊልንስቶን ሆምስ ባለቤት ኢንጅነር ጸደቀ ይሁኔ በቼስ ስፖርት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡ ተከታተሉን፡፡

 

አዲስ ዘመን፦ ቼስ ስፖርትን እንዴት ይገልጹ ታል?

ኢንጅነር ጸደቀ፦  ቼስ ስፖርት የተጫዋቾችን የማሰብ አቅም የሚያሳድግ፣ ጡንቻን ከማዳበር ይልቅ ለአዕምሮ ዕድገት እና ብስለት ብሎም ቅልጥፍና ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ከአራት እና ከአምስት እንቅስቃሴዎች በኋላ ማረፊያን አስቀድሞ መገመት የሚያስችል ስፖርት፣ ጥበብ እና መዝናኛም ነው፡፡ ቼስ ስፖርት ከጉልበት ይልቅ ወደ አዕምሮ ማበልጸግ እና ሥራ ማድላቱ ለተወዳጅነቱ ምክንያት ሲሆን ገደብ የለሽ ስፖርትም ነው፡፡ ገደብ የለሽ ያስባለው ደግሞ ቼስ በጾታ በዕድሜ እና በማንነት ላይ የማያተኩር ጡረታ የማይወጣበት ስፖርት ነው። ወቅታዊ ብቃት እስካለው ድረስ በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኝ ተጫዋችን የሚያሳትፍ ስፖርት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦  ቼስ ስፖርት በቀድሞ ሥራ አስፈጻ ሚዎች ሲመራ እና እናንተ ከመጣችሁ በኋላ ያሉትን ልዩነቶች በንጽጽር እንዴት ይገልጿቸዋል?

ኢንጅነር ጸደቀ፦ እንደምታውቀው እኛ ከመጣን አንድ ዓመትም አልሞላንም፡፡ ከእኛ በፊት የነበሩት ሥራ አስፈጻሚዎች በርካታ ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡ ብዙ እቅዶችንም አውጥተው ሰጥተውናል፡፡ እኛም የእነርሱን ጅምር እና የራሳችንን ዕቅድ አካተን ተግባራዊ ለማድረግ በስፋት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ቀደም ሲል ቼስ የተደበቀ እና ብዙ ሰው የማያውቀው ስፖርት እንደነበር ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ውስን ውድድሮች ቢደረጉም  በርካታ መገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ስፖርቱን ለማስተዋወቅ የተደረገው ጥረት እና የጽህፈት ቤቱ ባለሙያዎች ብርታት ታክሎበት መጠነኛ ለውጦች እየታዩ ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን፦  በዚህ ዓመት በዋነኝነት ምን ምን ለመስራት አስባችኋል?

ኢንጅነር ጸደቀ፦ እኛ ወደ ኃላፊነት ከመጣን ጀምሮ ዋና የትኩረት አቅጣጫችን አድርገን የያዝነው ውድድሮችን ማዘጋጀት እና ሀገር አቀፍ የሙያ ማሻሻያ ስልጠናዎችን ማጠናከር የመጀመሪያው ነው፡፡ የቀድሞ ሥራ አስፈጻሚዎች የጀመሯቸውን ቼስን በትምህርት ቤቶች እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማስፋፋት ሥራም ሌላው የትኩረት አቅጣጫችን አድርገን እየሄድንበት ነው፡፡ ቼስ ስፖርት ተወዳጅ እና ተዘውታሪ እንዲሆን በማድረግ በኩልም እንደዚሁ መጠነኛ ጥረቶችን እያደረግን ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ውድድሮችም ላይ መሳተፍ ችለናል፡፡ በ42ኛው የአዘርባጃን ባኩ ኦሊምፒያድ ላይ ተሳትፈን ልምድ ቀስመን መመለሳችን ይታወቃል፡፡ ከወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር እና ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር ባለን መልካም ግንኙነት አብሮ የመስራት መንፈስ ፈጥረናል፡፡ በቅርቡ በጅማ ከተማ ለምናካሂደው የአፍሪካ ዞናል 4 ነጥብ 2 የቼስ ውድድርም ሰፊ ትኩረት ሰጥተን ውጤታማ ውድድር ለማድረግ በትኩረት እየሰራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ ይህንን ውድድር በማስተናገዷ የምታገኘው ጠቀሜታን እንዴት መግለጽ ይቻላል?

ኢንጅነር ጸደቀ፦  በመጪው መጋቢት ወር ላይ የምናስተናግደውን የዞን 4ነጥብ 2 የቼስ ውድድር ከጅማ ቼስ ፌዴሬሽን ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመን ጅማ ከተማ ላይ እንዲካሄድ ወስነናል፡፡ በመጀመሪያ ኢትዮጵያ ይህንን ውድድር እንድታስተናግድ አመኔታ ማግኘቷ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቀደም ሲል ብዙ ውድድሮች በአዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ቢካሄዱም ከሌላው ጊዜ በተለየ ክልሎችም አህጉር ዓቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም እንዲፈጥሩ ያግዛቸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ውድድሩ በጅማ ከተማ መካሄዱ በርካታ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ በቅርቡ በሀገራችን ብዙ ችግሮች ተከስተዋል ብለው ሲያናፍሱ ለነበሩ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ምላሽ የምንሰጥበት ውድድር ነው፡፡ እንኳ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ቀርቶ እንደ ጅማ ባሉ የዞን ከተሞች ላይ እንኳ ምን ዓይነት ፀጥታ እና ሰላም እንዳለ ለመላ ዓለም በተለይም የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በመገንባት በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ከውጭ ሀገር ከሚመጡ ተወዳዳሪዎች እና የልዑካን ቡድን አባላት የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ደግሞ ሌላው ጠቀሜታ ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ለብዙ ኢትዮጵያውያን በውድድሩ ላይ የመሳተፍ ዕድል ይፈጥራል ብለን እንጠብቃለን፡፡ እርግጥ የእኛ ተወዳዳሪዎች ተሳትፎ የሚወሰነው በቅርቡ በምናካሂደው ክፍት ውድድር ላይ የሚያስመዘግቡት ውጤት(ሬት) ወሳኝነት አለው፡፡ በነገራችን ላይ በውድድሩ ላይ ግብጽን ጨምሮ 11 ሀገራት እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል፡፡

አዲስ ዘመን፦  ለምታዘጋጁት ክፍት ውድድርስ ምን ዓይነት ዝግጅት እያደረጋችሁ ነው?

ኢንጅነር ጸደቀ፦ በቅርቡ በምናዘጋጀው የክፍት የቼስ ውድድር ላይ በርካታ ተጫዋቾች እንደሚሳተፉ እንጠብቃለን፡፡ ይህንን ውድድር የምናካሂደው በጅማው ውድድር ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተጫዋቾችን ለማፍራት ነው፡፡ ጨዋታዎቹም ከሌላው ጊዜ በተሻለ በርካታ ተመልካቾች በውድድር ቦታዎቹ ላይ ተገኝተው እንዲከታተሏቸው፣ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን እንዲያገኙም ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ በጨዋታዎች ላይ ተመልካቾች መገኘታቸው በአንድ በኩል ጠንካራ ፉክክር ለማየት ያስችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለስፖርቱ ማደግም ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡

 አዲስ ዘመን፦  ኢንተርናሽናል ዳኛ እና አሰልጣኝ በማፍራት በኩልስ ምን ታስቧል?

ኢንጅነር ጸደቀ፦  በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ከተነሱ ክፍተቶች ውስጥ ዓለም አቀፍ ዳኛ እና አሰልጣኝ በማፍራት በኩል ያለው ውስንነት ነው፡፡ እኛም ይህንን ተረድተን ሰሞኑን ከየክልሉ ለተውጣጡ 17 ዳኞች የሁለተኛ ደረጃ የዳኝነት ስልጠና ሰጥተናል፡፡ በስልጠናው ላይ ከስድስት ክልሎች የተውጣጡ ቀደም ሲል የአንደኛ ደረጃ ስልጠና ወስደው በሥራ ላይ ያሉ ዳኞች ተካፍለዋል፡፡ ከዚህ ስልጠናም የተሻለ ብቃት ያሳዩ አምስት ያህል ዳኞችን መርጠን ውጤታቸውን እና ክህሎታቸውን ለዓለም አቀፉ ቼስ ፌዴሬሽን ልከን እውቅና ለማሰጠት በዝግጅት ላይ ነን፡፡ እንዳሰብነው ሆኖ መስፈርቱን አሟልተው ኢንተርናሽናል እውቅና የሚሰጣቸው ዳኞች ከተገኙ የዓለም አቀፍ ዳኞችን እጥረት የምንቀርፍ ይሆናል፡፡ በስልጠናው ላይ አምስት ክልሎች አልተሳተፉም፡፡ እነዚህ ክልሎች ያልተሳተፉበት ምክንያት ቼስ ስፖርት ባለመኖሩ ይሁን አይሁን ለማጣራትም እንሞክራለን፡፡ የቼስ ጨዋታዎችን የሚመሩ ዳኞች በተለያዩ ውድድሮች ላይ የተለያየ ውጤት ያስመዘግባሉ፡፡ ኢትዮጵያን ወክለው ዓለም አቀፍ የቼስ ጨዋታዎችን የሚመሩ ዳኞች ቁጥር መጨመሩ ደግሞ የሀገር ውስጥ ውድድሮች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን እንዲጠብቁ ከማድረግ ባሻገር ስፖርቱንም የማሳደግ እና የማስተዋወቅ ዕድል ይፈጥራል፡፡

አዲስ ዘመን ፦  በክለቦች ምስረታ ላይስ ምን ታስቧል?

ኢንጅነር ጸደቀ፦  ለቼስ ብቻ ሳይሆን ለየትኛውም ስፖርት የክለብ መኖር የውድድር መንፈሱ እንዲጠንክር እና ስፖርቱ አንድ እርምጃ ወደ ፊት እንዲራመድ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ የክለቦች ማቋቋምን የእኛ ሥራ አስፈጻሚ ቢያምንም በዚህ ዓመት ግን ከክለብ ምስረታ ይልቅ ቼስን በማስተዋወቅ እና በማስፋፋት ላይ ቅድሚያ ለመስጠት ከስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ በአንጻሩ በሚቀጥለው ዓመት በክለቦች ምስረታ ላይ ለመረባረብ አስበናል፡፡ በነገራችን ላይ ሰሞኑን የስድስት ወር አፈጻጸማችንን ገምግመን ነበር፡፡ የግምገማው ውጤት እንደሚያሳየው በአደረጃጀት በተለይም በቢሮ አወቃቀር ዙሪያ ላይ ክፍተት እንዳለ ተግባብተን ችግሩን ለመቅረፍም ወደ ሥራ ገብተናል፡፡
አዲስ ዘመን፦ የስፖርቱ ቁሳቁስ ውድ እና በገበያ ላይ አይገኙም ይባላል፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ኢንጅነር ጸደቀ፦ እውነት ነው፡፡ የቼስ ቦርድ እና ጠጠሮቹ ብሎም ሰዓቶቹ በሀገር ውስጥ አይመረቱም፡፡ ከውጭ ለማስገባትም ብዙ ውጣ ውርዶች አሉት፡፡ የስፖርቱ ቁሳቁስ ከቻይና በግዢ ስለሚመጡ ከቀረጽ ነጻ እንዲገቡ ያደረግነው ጥረት የለም፡፡ ሆኖም ግን ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የካስፓሮቭ ፋውንዴሽን የሰጠን 600 የቼስ ቦርዶች እና የመጫወቻ ጠጠሮች ግን እየመጡ ናቸው፡፡ እነዚህ የስፖርቱ ቁሳቁስ ሲመጡ በቁሳቁስ በኩል ያለው እጥረት በመጠኑም ቢሆን እንደሚቀረፍ እርግጠኛ ነኝ፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህ የእርዳታ ቁሳቁስ ከቻይና ስለሚገዙ ለማስመጣት የገጠመን ውጣ ውረድ ራሱ ቀላል አይደለም፡፡ አእምሮን የማበልጸግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለውን ቼስ ስፖርትን ለመጫወት የሚረዱት እና በዝቅተኛ ገንዘብ ለሚገዙት የተለየ የታክስ ህግ ቢኖር መልካም ነበር፡፡ በቀጣይ የስፖርቱ ቁሳቁስ በነጻ የሚገቡበትን መንገድ ለማመቻቸትም ውጥን ይዘናል፡፡
አዲስ ዘመን ፦ የታዳጊ ፕሮጀክት ስልጠናውስ ምን ላይ ደረሰ?
ኢንጅነር ጸደቀ፦ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ባለፉት ዓመታት ትኩረት ከሰጣቸው የስፖርት እንቅስቃሴዎች ውስጥ የታዳጊ ፕሮጀክት ስልጠናዎች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽንም ከሚኒስቴሩ የተሰጠውን ኮታ ታሳቢ አድርጎ ለታዳጊ ፕሮጀክት ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ በየክልሉ በርካታ የታዳጊ ፕሮጀክት ማሰልጠኛ ጣቢያዎችን ከማቋቋም ባሻገር በሚችለው አቅም ሁሉ ድጋፍ እና ክትትል እያደረገ ይገኛል፡፡ በነዚህ ጣቢያዎች ውስጥ ቁጥራቸው በቀላል የማይገለጽ ተተኪ ስፖርተኞች ስልጠናቸውን እየወሰዱ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፦ ባለሀብቱ ወደ ስፖርቱ መምጣቱ ጠቀሜታ አለው ብለው ያምናሉ?
ኢንጅነር ጸደቀ፦ እውነት ለመናገር ባለሀብቱ ወደ ስፖርቱ መምጣቱ ለስፖርቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ስፖርት በግልጽነት የምትሰራበት፣ ህዝብን ለማርካት ውክልና የምትወስድበት ትልቅ ተቋም ነው፡፡ ስለሆነም ባለሀብቱ እጠቀማለሁ ብሎ ወደ ስፖርት አይመጣም፡፡ ሆኖም ግን በማስተዋወቅ በኩልም ቢሆን በተያያዥነት የሚመጡ ጥቅሞች ሊኖሩ እንደሚችሉ እረዳለሁ፡፡ ለምትመራው ስፖርት ህዝባዊ ሆነህ ተቀባይ ሳትሆን ሰጪ መሆን፣ በፌዴሬሽኑ በኩል የሚደረጉ ስብሰባዎችን ያለማቋረጥ መከታተል፣ በጽህፈት ቤቱ የሚቀርበውን ሪፖርት ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር መወያየት እና ስፖርቱን ለመገናኛ ብዙሃን ክፍት በማድረግ ለትችት እና ለአድናቆት በር መክፈት ከስፖርት አመራሮች የሚጠበቅ ቁልፍ ሥራ እና ኃላፊነት መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፦ ስፖርቱን ለማስፋፋት የሚፈቀድላችሁ በጀት በቂ ነው ማለት ይቻላል?
ኢንጅነር ጸደቀ፦ እውነት ለመናገር የሚመደብልን በጀት በቂ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ሆኖም ግን የሀገሪቱን የኢኮኖሚ አቅም ከግንዛቤ ውስጥ ስናስገባ ተጨማሪ በጀት ከመጠየቅ ይልቅ ውድድሮችን በማብዛት ጨዋታዎችን መሸጥ እና ስፖንሰር ማፈላለግ ላይ ማተኮር እንደሚገባን ተማምነናል፡፡ የሚመደብልን በጀት ቢጨምር አንጠላም፡፡ ሆኖም ግን ይቺን መጠነኛ በጀት እንኳን ስንጠይቅ እያፈርን ነው፡፡ እንደምታውቀው ብዙ ስፖንሰር አድራጊዎች መጠጦች እና ምግብ አቅራቢዎች ናቸው፡፡ እኛም እነዚህን ድርጅቶች ጭምር ስፖንሰር ለመጠየቅ ፕሮፖዛሎችን አዘጋጅተን ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ እንደሚሳካልንም እርግጠኛ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፦ አመሰግናለሁ፡፡
ኢንጅነር ጸደቀ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡  

 

ታምራት አበራ

Published in ስፖርት
Sunday, 05 February 2017 19:34

ከሁሉ ተጋባ

ባልደረባዎችህ...

            ስትገባ መሥሪያ ቤት አንተኑ ያማሉ፣

            እድር ባዩ መጣ እያሉ ያወራሉ።

ወዳጆቼ ያልካቸው...

            ሊጋብዙህ ጠርተው ቤታቸው ስትገባ፣

            ይሉሃል አይሰጥም ንፉግ ነው ገብጋባ።

ታክሲ ስትሳፈር...

            ረዳቱ ሲያይህ ገና ሳለህ ከሩቅ፣

            ይላል መጣላችሁ ደግሞ ሊጨቃጨቅ።

የሰፈሩ ሴቶች...

            ስትገባ ስትወጣ መንገድህ ላይ ያሉ፣

            ሰላምታ እንኳ  የማያውቅ ኩራተኛ ይላሉ።

ሌላው ሌላው ቀርቶ...እኚያ ዘመዶችህ

            ባትሄድ ከቤታቸው አሉህ ወረተኛ፣

            ዛሬ ሲሞላለት ተረሳነው እኛ።

ውዴ...ግና እኔ ሳውቅህ

            አድር ባይ አይደለህ ቃልህን አክብረሃል፣

            ስትኮራ አላየሁም ለእኔ እሺ ብለሃል።

ሰስተህ ነፍገኸኝ አታውቅም በእውነት፣

            ሰምቼም አላውቅም ክፋት ከአንተ አንደበት።

            በወረት ተይዘህ አላየሁም እኔ፣

            ትተኸኝ አታውቅም ርቀህ ከጎኔ።

            ታዲያ ምነው አሉ?

            የምወድህ አንተን እንደዚህ ያማሉ፣

...ቢያውቁህ ኖሮ እንደእኔ መች እንዲህ ይላሉ።

ወይ!

            ሰላም ከምታጣ ስትወጣ ስትገባ

            እሺ በለኝና ከሁሉም ተጋባ

            እኔን አይከፋኝም ሁሉንም አግባቸው

            ሚስትህ ሲሆኑ እንደው...ጥሩ የሆነ ጎንህ ጎልቶ የሚታያቸው።

 

ሊድያ ተስፋዬ

Published in መዝናኛ
Sunday, 05 February 2017 19:33

ታስሯል

እሪ አሉ፤ ጩኸታቸውን አሰሙ። እሪታና ጩኸትን ምን ለያቸው አትበሉኝ፤ ብቻ ነገሩ ምን ያህል ግዙፍ እንደሆነ እንድትረዱልኝ ስል ነው። እና! የጋራ መኖሪያ የሆነው ኮንዶሚኒየም የቀድሞ ጉርብትናን ቀንሷል ለሚሉ ይብላኝላቸውና እኛ የእኚህ እናት ጎረቤቶች፣ የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎች ግን ስብስብ ብለን ከየቤታችን ወጣን። ቢያንስ በሙቀጫ ቡና ሲወቀጥ እና ሰው ድምጹን ከፍ አድርጎ ሲጮህ ይሰማላ!

እሪታቸው ቀጥሏል። እኔን ጨምሮ በርከት ያልን ግን ጥቂት ሰዎች ከበብናቸው። በርከት ብሎ ጥቂት መሆን እንዴት ነው? ይህ በሁለት አንጻር ሊታይ ይችላል፥ አንጻር አንድ፣ ኮሽ ሲል ግር ብሎ አካባቢውን የጥምቀት በዓል የሚያስመስል ብዙ ሰሚና ተመልካች አለ፤ በዛ መልኩ ከታየ ጥቂት ሰዎች ነን። አንጻር ሁለት፣ ለጋራ መኖሪያ ቤት፣ ያውም በሥራ ቀን በቤት ውስጥ እንደተገኙ ሰዎች ብዙ ነን።

«ምንድን ነው? ምን ተፈጠረ? እማማ ምን ሆነው ነው?» አለች አንዲት ሴት ከመካከላችን፣ «ምን አይደለም፤ እማማ አልሰማ ብላኝ ነው» አለችን አንዲት የቀይ ዳማ ሳቂታ ፊት ያላት ወጣት፤ አጠገባቸው ቆማ ወደ ውስጥ እንዲገቡ እና ዝም እንዲሉ ለማድረግ እየጣረች እንደሆነ ታስታውቃለች።

«ኧረ ተውኝ፤ ደግሞ አልሰማ ብላኝ ትያለሽ? ልጄን...ታስሯል ብለሽኝ ስታበቂ አልሰማ አለች ትያለሽ?» አሉ ሲቃ በተመላ ድምጽ። ያሳዝናሉ፤ ልጃቸው ታስሮባቸው እንደሆነ ገመትሁ ወይም አወቅሁ። ሁላችንም ማለት ይቻላል ከንፈራችንን መጠጥን፤ የመጀመሪያ እርዳታ አይደለ የሚባለው!?

«አይዞት እማማ! ይፈታል፤ ፈጣሪ ያውቃል፣ አይዞት ይበርቱ» አንድ ሌላ ሴት ናት፤

«መቼ ነው የሰሙት?» አለ ከመካከላችን የቆመ አንድ ጎልማሳ ሰው፤ «አሁን ነው የሰማሁት፤ ከኖርኩበት ቀዬ የመጣሁ ከትላንት በስቲያ ነው፤ ልጄን ለማየት ነው መምጣቴ፣ ታዲያ ይህቺ እህቱ ይኸው በእርሷ ቤት ተደብቃ ማውራቷ ነበር፤ ታስሯል ስትል ሰማሁ፤ ደግሞ መልሳ አልታሰረም ማለቷ፤ ኧረ የእኔስ ነገር... ልጄን...ቅመሜን... አገልጋዬን...» ማልቀስ ጀመሩ።

«አንቺ ቀስ ብለሽ አትነግሪያቸውም ነበር እንዴ? ወደ ከሰዓት ላይ ብታደርጊው እንኳን ምን ነበር?» አንዲት ሴት ቆጣ ባለ አነጋገር ተናገረች። ሁላችንም እኩል ሃሳብ እንደመጣላቸው ሰዎች እኩል አወራን። አንድ ሶስት ሰዎች ንግግራቸውን ሳያቋርጡ ከራሳቸው ጋር እየተነጋገሩ ሄዱ፣ የቀረነው ቀረን። «በቃ እናት፤ ሄደው ይጠይቁት፤ ምንም አይሆንምኮ! መረጋጋት ነው የሚያስፈልገው፤ አያስቡ» አልኩኝ፤ ሃሳብ መስጠቱ ለምን ይቅርብኝ!?

«አያስቡ? እና ምን ላድርግ? ከተሜዎች ደግሞ አታስቡ ማለት ትወዳላችሁ፤ እና ካላሰብኩ ምን ልሆን ነው? ጭንቅላት የተሰጠው ለማሰብ ነውና አስባለሁ፤ ደግሞስ ጭራሽ ልጄ ታስሮብኝ አላስብ?» ለቅሷቸው ከንዴት ጋር ተባብሮ በረታ፤ አብራቸው የቆመችው ልጅ ስልኳን ትጎረጉራለች። በዚህ ሁኔታ መቼም ከሰው ጋር መልዕክት አትላላክም፤ ምን እያደረገች ይሆን? መጨረሻውን ለማየት ጓጓሁ።

«በቃ ይኸው ታናግሪዋለሽ፤ እኔን አላምን አልሽኝ አይደለ? ከራሱ አንደበት ስሚው» ብላ ስልኩን ከእኚህ ባልቴት ጆሮ ላይ ደቀነችው። «አትቀልጂብኝ ባክሽ ልጄ፤ ተይ አትቀልጂብኝ» እንባ የሌለው ለቅሷቸው ድንገት ጸጥ አለ።

«ንገረኝ ምሳዬ! ታስረሃል አይደለ? ይህቺ ቀጣፊ እህትህ አልነግር ብላኝ ነው? ታስረሃል?» ጠየቁ፤ ከዛኛው መስመር የሚወጣው ድምጽ ባይሰማንም ታስሯል ያሉት ልጃቸው እንዳልታሰረ ማረጋገጣቸውን ግን ከገጻቸው ፈገግታ ላይ እኛ ጎረቤቶቻቸው አይተናል። «ተው! እስቲ ሙች ብለህ ማልልኝ» ልጃቸው አጠገባቸው ያለ ይመስል የግራ እጃቸውን መዳፍ ወደፊት ዘረጉት፤ ፈገግታቸው ጨመረ፤ ግን ቶሎ አላመኑትም።

«እስኪ እከሌ ይሙት በል...» «እስኪ ከእከሌ ይለየኝ በል...» «እስኪ...» እንደው ጉዳዩ ላይ በታዛቢነት እንደጀመርኩ በታዛቢነት ልጨርስ ብዬ እንጂ እኚህ ባልቴት እናት ለተወሰነ ደቂቃ ታስረሃል አላምንህም ብለው ከልጃቸው ጋር ተከራክረዋል። የእናት ነገር፣ «እንደ እናቴ አይደለ እንደ ሚስቴ አውለኝ» ይሉት ብሂል ትዝ አለኝ። በመጨረሻ ግን እኚህ እናት ልጃቸው ያለመታሰሩን አመኑ።

«ጎሽ... በል ታዲያ ለምን ነው መጥተህ የማታየኝ፤ ደግሞስ ይህቺ እህትህ ማንን ነው ታሰረ የምትለው?»

«እኮ! ምን አውቃለሁ፤ ምሳዬ ታስሯል ስትለኝ ነዋ! ልጄ! ያን ያልኩህን...» ስልኩን ከጆሯቸው ላይ ሳይነቅሉ ወደ ቤት ውስጥ ገቡ። ከበራቸው አፍ ላይ ከቀረነው መካከል እኔ ቀረሁና ሌሎቹም እርስ በእርስ እየተነጋገሩ ሄዱ።

«ምንድን ነው የተፈጠረው?» አልኳት። ምንአልባት ከሌሎች ጎረቤቶቻችን የተሻለ ነገሮችን የማጣራት ፍላጎት እንዳለኝ አስባ ይሆናል፤ ግን ነገሩን ሁሉ አብራርታልኛለች፥ ያለችኝንም እንዲህ ልንገራችሁ፥ እማማ ብቸኛ ወንድ ልጃቸው ነውና ከአንጀታቸው ነው ልጃቸውን የሚወዱት። በእርግጥ ሰዎች ናቸው፤ «ከአንጀትዎ ነው ልጅዎን የሚወዱት» የሚሏቸው እንጂ መውደዳቸው ከአንጀታቸው ይሁን ከየት አያውቁም፤ ብቻ ግን ከራሳቸውም አብልጠው ይወዱታል። የሚጦራቸው እርሱ ነው፤ የሚያለብሳቸውም እርሱ፤ በሚኖሩበት ከተማ ካለው የእርሻ ማሳ በላይ ልጃቸው መጋቢያቸው እንደሆነ ያምናሉ። እንደውም ገና ሲያዩት እንደሚጠግቡ ገለጸችልኝ። ለዛም ምሳዬ እንዳሉትም ነው ያወጋችኝ።

ታዲያ በዚህ ቀን ማለዳ ይህቺ ልጅ ድንገት ተነስታ በስልክ እየተነጋገረች «ምሳዬማ ታስሯል...መጣሁ» አለች። እናቷ «ልጄ፤ ምሳዬ ታስሯል» አሉ፤ እርሷ ደግሞ ምሳ የሚጋብዘኝ አልፈልግም፤ ምሳ ይዣለሁ ማለቷ ነበር።

 

ሊድያ ተስፋዬ

Published in መዝናኛ

ዶክተር ኤሊያስ አቢሻክራ፤

 

     የዛሬው የህይወት እንዲህ ናት አምዳችን እንግዳ  ዶክተር ኤሊያስ አቢሻክራ ናቸው፡፡ ዶክተር ኤሊያስ በካራቴ ስፖርት ውስጥ ከ40 ዓመት በላይ ያሳለፉ እና የፈረንሳይ ካራቴ ፌዴሬሽን ዳን ፈታኝ የነበሩ ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው፡፡ 37 ዓመታትን ያህል ፈረንሳይ ያሳለፉት የቀድሞ የአሎሎ እና የዲስከስ ውርወራ ውጤታማ ተወዳዳሪው ዶክተር ኤሊያስ በብዙ ውጣ ውረዶች የተፈተነውን የ61 ዓመት የህይወታቸው ጉዞን እያወጉን ይዘልቃሉ፡፡  መልካም ንባብ፡፡ 

 

ውልደት እና ዕድገት

በ1923 ዓ.ም አጼ ኃይለስላሴ ወደ ስልጣነ መንበሩ ሲመጡ ትኩረት ከሰጧቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ትምህርት ነበር፡፡ የሀገሪቱን ህዝብ በትምህርት ማነጽ ዓላማ አድርገው የተንቀሳቀሱት ንጉሱ ከተለያዩ የውጭ ሀገራት በርካታ መምህራንን አስመጡ፡፡ ከነዚህ መምህራን መካከል የዛሬው እንግዳችን ኤሊያስ አቢሻክራ አባት ሳሊም አቢሻክራ ይገኙበታል፡፡ ሳሊም አቢሻክራ ሊባኖሳዊ ሲሆኑ አዲስ አበባ መጥተው በተፈሪ መኮንን፣ በበየነ መርዕድ እና በመድሃኒያለም ትምህርት ቤቶች በዳይሬክተርነት እና በመምህርነት አገልግለዋል፡፡

መምህሩ ሳሊም አቢሻክራ ከስራቸው ጎን ለጎን የፍቅር ጓደኛ ፍለጋ ሲኳትኑ ከወይዘሮ ሸዋዬ ሮሪሳ ጋር ተዋወቁ፡፡ ከእንስቷ ጋር ትውውቃቸው አድጎ ሶስት ጉልቻ መስርተው መኖር ጀመሩ፡፡ በሁለተኛ ዓመታቸውም ሰኔ 28 ቀን 1941 ዓ.ም የበኩር ልጃቸውን ኤሊያስ አቢሻክራን ወደዚች ምድር  አመጡ፡፡ ኤሊያስ በተሻለ የኑሮ ደረጃ ከሚገኙ ቤተሰቦች በመወለዱ ምንም ሳይጎድለበት የፈለገው እየተሟላለት፣ የጠየቀው እየተመለሰለት አዲስ አበባ በተለምዶ አጠራር የድሮው ቄራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለእርሱ አርዓያ በሆኑት ወላጆቹ ይህ ቀረሽ የማይባል እንክብካቤ ተደርጎለት አደገ፡፡

ፊደል ቆጠራ

የአጼ ኃይለስላሴ መኮንኖችንም የፈንጅ ኬምስትሪ ያስተምሩ የነበሩት አባቱ ሳሊም አቢሻክራ ልጃቸው ላመነበት ነገር ትግል እንዲያደርግ፣ በራሱ የሚተማመን እና ሀገሩን እና ታሪኳን ጠንቅቆ የሚያውቅ ዜጋ እንዲሆን በተደጋጋሚ ምክር ይለግሱት ነበር፡፡ ህጻኑ ኤሊያስ እድሜው ለትምህርት ሲደርስም በ1946 ዓ.ም በአምስት ዓመቱ የአሁኑን ናዝሬት የልጃገረዶች ትምህርት ቤትን ተቀላቀለ፡፡  በናዝሬት ትምህርት ቤት ብዙም ስላልተመቸው በ1948 ዓ.ም  ወደ ልደታ ትምህርት ቤት ተዛወረ፡፡ በአጼ ኃይለስላሴ ታምኖባቸው ኢትዮጵያዊ ዜግነት የተሰጣቸው ሳሊም አቢሻክራ ልጃቸው ሁልጊዜም የተሻለ ትምህርት እንዲያገኝ ጽኑ ፍላጎት ስለነበራቸው ከአራት ዓመት የልደታ ትምህርት ቤት ቆይታ በኋላም ወደ ዘጠነኛ ክፍል ሲዛወር ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት አስገቡት፡፡

ተማሪ ኤሊያስ በቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት 9ኛ እና አስረኛ ክፍልን ከተማረ በኋላ ከመምህራን ጋር በተፈጠረ አለመግባባት በ1956 ዓ.ም ወደ ሊሴ ትምህርት ቤት ተዛወረ፡፡ሳሊም ልጃቸው ፈረንሳይኛ ቋንቋ እንዲያውቅ እና ከምንጊዜውም የተሻለ ትምህርት እንዲያገኝ አስበው በወቅቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ልጆች በሚማሩበት ሊሴ ትምህርት ቤት ቢያስገቡትም ነገሮች ሁሉ እንዳሰቡት አልሆነላቸውም፡፡

ምንም ዓይነት የፈረንሳይኛ ቋንቋ ችሎታ ሳይኖረው በሌላ ትምህርት ቤት 10ኛ ክፍል የደረሰው ኤልያስ  11ኛ ክፍልን ከመቀጠል ይልቅ ወደ ታች ወርዶ ከስድስተኛ ክፍል ትምህርቱን እንዲጀምር በሊሴ ትምህርት ቤት አስተዳደር ተነገረው፡፡ ኤልያስም ይሁን ቤተሰቦቹ የትምህርት ቤቱን ውሳኔ ተቀብለው ዝቅ ብሎ ከስድስተኛ ክፍል  ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ በሊሴ ትምህርት ቤት ቆይታው በጠቅላላ እውቀት ጥያቄዎች ላይ በተደጋጋሚ ተሳትፎም አሸናፊ ሆነ፡፡እስከ 1963ዓ.ም ድረስ የሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ትምህርቱን ከተማረ በኋላ የ12ኛ ክፍል የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ወስዶ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቡ ፈረንሳይ ሀገር ሄዶ «ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኦርሊንዝ» ለመማር የሚያስችለውን ውጤት አስመዘገበ፡፡

 ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኦርሊንዝ

የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተናውን በድል የተወጣው የ24 ዓመቱ ኤሊያስ በ1965ዓ.ም አዲስ አበባን ለቆ በፈረንሳይዋ ኦርሊንዝ ከተማ መዳረሻውን አደረገ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤተሰቡ ርቆ ብቻውን መኖር የጀመረው ኤልያስ በፈረንሳይኛ አቀላጥፎ ለመግባባት አልተቸገረም፡፡በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ብሎም ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል አፍሪካውያንን ማግኘቱ ኤልያስ በቀላሉ ኦርሊንዝን እንዲለምድ ረዳው፡፡በፈረንሳይ ማዕከላዊ ግዛት ዋና ከተማ ኦርሊንዝ ማረፊያውን ያደረገው ኤልያስ ነጻ የትምህርት እድል የሰጠውን «ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኦርሊንዝ» የህክምና ትምህርት እንዲያስተምረው ቢጠይቅም አሻፈረኝ ተባለ፡፡ ሀገር አቋርጦ ፈረንሳይ ማረፊያውን ያደረገው ኤልያስ በእርሱ ምርጫ ሳይሆን በዩኒቨርሲቲው ምርጫ የህግ ትምህርት ቤትን እንዲቀላቀል ተደረገ፡፡ ከአለባበስ ጀምሮ ሰፊ ጥንቃቄ የሚጠይቀው የህግ ትምህርት ለኤልያስ በግዴታ የተጫነበት የማይፈልገው የትምህርት መስክ ቢሆንበትም አማራጭ ስላልነበረው ለሁለት ዓመት የህግ ትምህርቱን ተከታተለ፡፡ እንደጠላውም በህግ ትምህርቱ ውጤታማ መሆን ሳይችል ቀርቶ አቋረጠው፡፡ ወዲያውኑም ወደ ጂኦግራፊ ትምህርት ፊቱን አዞረ፡፡ «በነገራችን ላይ የፈረንሳዮች የትምህርት ፖሊሲ ለየት ያለ ነው፡፡ ዲግሪ ለመማር የሚያስፈ ልገው የመግቢያ ፈተና ማለፍ ብቻ ነው፡፡ የማስተርስ ዲግሪ ግን ጥናታዊ ጽሁፍ መስራትን ይጠይቃል፡፡ እኔም ጂኦግራፊ ለመማር የሚያስችለኝን ፈተና አለፍኩ ማለት ነው» ሲልም ይገልፃል።

 በጂኦግራፊ የትምህርት መስክ የባችለር ዲግሪውን ለመከታተል የሚያስችለውን መግቢያ ፈተና ያለፈው ኤልያስ በ1967ዓ.ም  ትምህርቱን ጀመረ፡፡ ከአራት ዓመት በኋላ በ1970ዓ.ም ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኦርሊንዝ ዲግሪውን እና ማስተርሱን ተቀበለ፡፡ ህክምናን ፈልጎ በጂኦግራፊ የተመረቀው ኤልያስ ማስተርሱን ከያዘ በኋላ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ትውልድ ሀገሩ ኢትዮጵያ ሊመለስ ወሰነ፡፡ የመመለሻ ቀን ቆርጦም ቤተሰቦቹ እንዲቀበሉት በደብዳቤ ገለጸ፡፡

ይሁን እንጂ ከሀገር ቤት የመጣለት የደብዳቤው ምላሽ ግን ኤልያስን የሚያስደነግጥ ነበር፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው አለመግባባት እና ቀይ ሽብር መስፋፋት ምክንያት ኤሊያስ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንደሌለበት የሚገልፅ ምላሽ ተሰጠው፡፡ «ቀደም ሲል መጥተህ ናፍቆቴን የምወጣበት ቀን ርቆብኛል ስትል የነበረችው እናቴ አዲስ አበባ መጥተህ ከሚገድሉህ እዚያው ሁንና ቢያንስ በህይወት አለ ብል ይሻላል የሚል ደብዳቤ ጻፈችልኝ፡፡ ቀደም ሲል ናፍቄያት የነበረችው እናቴ ስትጨክን እኔም ችግር እንዳለ ተረዳሁ፡፡ ይሁን እንጂ ፈረንሳይ ውስጥ ለመኖር መማር ግድ ስለሆነ መማርን ሳልወድ አማራጭ አድርጌ ወሰድኩት» ይላል።ስለሆነም በጂኦግራፊ ትምህርት የፒኤችዲ ፕሮግራሙን ጀመረ፡፡ከዚህ ወጣቱ በትምህርትም በእድሜም እየበሰለ በመሄዱ አንቱታን ተጎናፀፈ።

ምሁሩ የጉልበት ሰራተኛ

የቤት ኪራይ እና የምግብ ወጪ አላወላዳ ስላላቸው ያገኙትን ስራ ለመስራት ወሰኑ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ የጠየቁትን እና የተመኙትን እያገኙ ቢያድጉም የኦርሊንዝ ኑሮ ግን ከእጅ ወደ አፍ ብሎም የሰው እርዳታን የሚያሻ ሕይወት ሆነባቸው፡፡ የዶክትሬት ትምህርታቸውን ከጀመሩ በኋላ ቀደም ሲል ያጡትን ድጋፍ በራሳቸው ለመወጣት ደፋ ቀና ማለት ጀመሩ፡፡

ማስተርስ ዲግሪያቸውን ከጨረሱ በኋላ የትኛውንም ወጪ በራሳቸው መሸፈን ግዴታ ውስጥ የገቡት ባለ ተስፋው ኤሊያስ በአንድ ጎሚስታ ቤት በቀን ሰራተኛነት ተቀጠሩ፡፡ ነገር ግን ስራው ከትምህርታቸው ጋር ስላልተመቻቸው ቀይረው በአንድ ነዳጅ ማደያ ድርጅት ውስጥ በቤኒዝን ቀጂነት ተቀጠሩ፡፡ በእነዚህ ስራዎች ያልተገደቡት አቶ ኤልያስ በሀገሪቱ ዝቅተኛ ስራ ተደርገው የሚቆጠሩትን ስጋ መመዘንን እና ፎቶ የማንሳት ስራዎችም ሰርተዋል።ይሁን እንጂ በመሀል የቅርብ አማካሪያቸው እና የፒኤችዲ ትምህርቱን ያስጀመራቸው የቅርብ ጓደኛቸው እና አስተማሪያቸው ኦርሊንዝ ከተማን ለቆ ወደ ሌላ ከተማ መዛወሩን ሲነግራቸው ይበልጥ ተስፋ ቆረጡ፡፡

ነገር ግን በአዲስ አማካሪ የፒኤችዲ ጥናታዊ ጽሁፋቸውን ማዘጋጀት ጀመሩ፡፡ ስምንት ዓመት ያህል ፒኤችዲ ትምህርታቸውን ተከታትለው ለመመረቅ ጫፍ ላይ ቢደርሱም ጥናታዊ ጽሁፉን ለማሳተም የሚያስችል ገንዘብ የሌላቸው መሆኑን ደግሞ  ሌላ ሀዘን ውስጥ ገቡ፡፡ ሆኖም ግን ጓደኞቻቸው ጥናታዊ ጽሁፉን ለማሳተም የሚያስችል እርዳታ እንደሚያደርጉላቸው ቃል ሲገቡላቸው ተስፋ ቆርጠው የነበሩት ምሁር እንደገና ወኔ ተሰማቸው፡፡ እርሳቸውም የተቻላቸውን ገንዘብ ለመቋጠር ቀን ከሌሊት ደፋ ቀና ማለት ጀመሩ፡፡ በመጨረሻም 300 ገጽ ያለው ጥናታዊ ጽሁፉቸው ታትሞ ለምርቃት በቁ፡፡

  በአራት ዓመት ውስጥ ፒኤችዲ ዲግሪያቸውን ማግኘት የነበረባቸው ዶክተር ኤሊያስ የጥናታዊ ጽሁፋቸው አማካሪ እርሳቸው ከሚኖሩባት ኦርሊንዝ ከተማ 100 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ መኖሩ እና እርሳቸው በቅርብ ርቀት ማግኘት ስላልቻሉ ስምንት ዓመት ወስዶባቸው በ1978ዓ.ም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተቀበሉ፡፡

 የስራ አሰሳ

  የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን የተረከቡት ዶክተር ኦልያስ በተመረቁ ማግስት የተሻለ ስራ አገኛለሁ ብለው ተስፋ ቢያደርጉም ከኦርሊንዝ ከተማ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመምህርነት ስራ አገኙ።ነገር ግን የስራውን ክብደት ስለተረዱ ማስተማር እንደማይፈልጉ ገለጹ፡፡

   ኢትዮጵያን ለውጭዎች

   ዶክተር ኤልያስ እንደ ካምብሪጅ ከመሰሉ ጠንካራ ዩኒቨርሲቲዎች ተርታ በሚመደበው ፓሪስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስለ ኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ለመጻፍ የሚፈልግ አንድ ምሁር በጓደኛቸው በኩል አገኛቸው፡፡ በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ ስለ ኢትዮጵያ ስፖርት ከማወቅ ባሻገር ስፖርተኛ እንደነበሩም ነግረውት የኢትዮጵያን ስፖርት ታሪክ ምንም ሳያስቀሩ ነገሩት፡፡ ‹‹ተማሪው ካሰበው በላይ ሰፊ መረጃ ሰጠሁት፡፡ የሰጠሁትን መረጃ ጽፎ እኤአ በ2004 በግሪክ አስተናጋጅነት በተካሄደው 28ኛው የአቴንስ ኦሊምፒክ ላይ በግሪክ ቋንቋ ተተርጉሞ መቅረቡንም ነግሮኛል፡፡ እኔ ከዚህ ባሻገር ስለ አባይ እንዲሁም ከጥቂት ዓመታት በፊት የተነሳው የአረቦች አብዮት ኢትዮጵያን እንደማያሰጋት የሚያሳዩ በርካታ ጽሁፎችን እና ትንታኔዎችን አቅርቤያለሁ፡፡ እነርሱም ለነዚህ ስራዎቼ ተገቢውን ክብር ሰጥተውኛል፡፡››      በማለት በኦርሊንዝ ቆይታቸው ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ በኩል ያደረጉትን አስተዋጽኦ ይገልጻሉ-ዶክተር ኤልያስ፡፡

ስፖርት

ዶክተር ኤልያስ ገና በህፃንነታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እያሉ በ100 ሜትር ሩጫ፣ በአሎሎ እና በዲስከስ ውርወራ ይሳተፉ ነበር፡፡ ቀደም ሲል ኢትዮጵያን ወክለው ኬንያ ሄደው በአሎሎ ውርወራ መሳተፍ ችለዋል። በ1963ዓ.ም በተካሄደው የተማሪዎች ውድድር ላይ ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤትን ወክለው በአሎሎ እና በዲስከስ ውርወራ ተሳትፈው በአንደኝነት አጠናቀዋል፡፡ በተመሳሳይ በ100 ሜትርም ሶስተኛ ሆነው ነበር ሩጫቸውን የጨረሱት፡፡ ክብረ ወሰን በማሻሻል ያሸነፉት የቀድሞ ተማሪ የአሁኑ ዶክተር ኤልያስ በእለቱ በተገኙት የክብር እንግዳ አጼ ኃይለስላሴ 38 ቁጥር ጫማ ሲሸለሙ ከመደሰት ይልቅ ቅሬታ ተሰማቸው፡፡«ሌላ ጊዜ ጃንሆይ በውድድር ቦታ ሲመጡ ለአሸናፊዎች የወርቅ ሰዓት ወይም ብዕር ይሸልሙ ነበር፡፡እኔ 42 ቁጥር ጫማ እያደረኩ 38 ቁጥር ሸለሙኝ፡፡ እኔ የምጠብቀው የወርቅ ብዕር ወይም ደግሞ ሰዓት ስለነበር ተናድጄ ወጣሁ»ይላሉ ዶክተር ኤልያስ የቀድሞ የስፖርት ትዝታቸውን ሲያወጉ፡፡

በነጋታው ግን መልካም ዜና ሰሙ፡፡አጼ ኃይለስላሴ በውድድሩ ላይ ያሸነፉ አትሌቶች በቤተ መንግሥት ግብዣ እንደሚደረግላቸው መጥራታቸው ተነገራቸው፡፡«ጥሪውን እንደሰማሁ ከእናቴ ጋር ቀጥታ ወደ መርካቶ ሄደን ሙሉ ልብስ ገዛችልኝ፡፡ አባቴም ንጉስ ፊት ስቀርብ ጀርባ መስጠት እንደሌለበኝ እና አጠቃላይ ማድረግ ያለብኝን ሁሉ ነገረኝ፡፡ ቤተ መንግሥት ገብቼም ከተጋበዝን በኋላ የወርቅ ሰዓት ተሸልሜ ተመለስኩ፡፡ ይህ ሽልማት ለእኔ ከፍተኛ ብርታት ሰጠኝ፡፡»

ስፖርትን በፈረንሳይ

ዶክተር ኤልያስ በኦርሊንዝ ዩኒቨርሲቲ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በዩኒቨርሲቲው አትሌቲክስ ክለብ ውስጥ በአሎሎ እና ዲስከስ ውርወራ ዘርፍ ልምምድ መስራት ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጂ ስልጠናው የሚሰጥበት ቦታ ከኦርሊንዝ ከተማ ወጣ ብሎ በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ስለነበር ለትራንስፖርት ችግር እና ለተጨማሪ ወጪ ስለተዳረጉ ከሚወዱት ስፖርት ወደ ሌላ ስፖርት ፊታቸውን ለማዞር ተገደዱ፡፡ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ የካራቴ ተማሪዎች ስልጠና ሲወስዱ ተመልክተው በካራቴ ስፖርት ተሳቡ፡፡ አርፍደውም ቢሆን ካራቴ ስፖርትን በጀማሪ ሰልጣኝነት ተቀላቀሉ፡፡ ስልጠናቸውን አጠናክረው ከወሰዱ በኋላ ዩኒቨርሲቲያቸውን በመወከል በበርካታ ሻምፒዮናዎች ላይ የመሳተፍ እድል አገኙ፡፡

ከአንድ ዓመት በኋላ በ1966 ዓ.ም ወደ አሰልጣኝነት ገብተው ማሰልጠን ጀመሩ፡፡ ብዙዎች እረፍት በሚያደርጉበት ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ 4 ሰዓት ድረስ ለማስተማር ዋና አሰልጣኛቸውን ጠይቀው ፈቃድ በማግኘታቸው ማሰልጠን ጀመሩ፡፡ ከዓመት በኋላ ኦርሊንዝ ከተማ የሻምፒዮናው አዘጋጅ ስትሆን ተሳትፈው ሁለት ጣቶቻቸው ወልቀው፣ ሁለት ጎድኖቻቸውም ተሰብረው መጫወት ስላልቻሉ በፎርፌ ከግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ውጭ ሆኑ፡፡

በዚህ መሀል የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ወደ ሌላ ከተማ መኖሪያቸውን ቀይረው ሲሄዱ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላቸው ዋና አስተማሪ ሆነው ቢቀጥሉም ከ120 ተማሪዎች ውስጥ አብዛኛው ሰልጣኝ ወደ ሌላ ክለብ በመዘዋወራቸው የቀሩትን 30 ብቻ ተማሪዎች ይዘው የካራቴ ስልጠናውን ገፉበት፡፡ አብዛኛው የፈረንሳይ ካራቴ ተወዳዳሪ ከ18 ዓመት እስከ 28 ዓመት እድሜ ያለው ቢሆንም እርሳቸው ግን ጥቁር ቀበቶ የያዙት እንኳ በ29 ዓመታቸው ቢሆንም በ30 ዓመታቸው ወደ ውድድር ገቡ፡፡ እስከ 40 ዓመታቸውም በተለያዩ ውድድሮች ላይ የመሳተፍ እድል አግኝተዋል፡፡

ዶክተር ኤልያስ የካራቴ ስፖርትን ገፍተውበት ጃፓናዊ የካራቴ ስፖርት መስራች ሰንሴይ ኦሺማ የሚሰጡትን የካራቴ ዳኖች መፈተን ጀመሩ፡፡ የኦሺማን ሁለተኛ ዳን/ዲፕሎማ/ በ1972 ዓ.ም እንዲሁም በ1978ዓ.ም ሶስተኛ ዳን እና ከጂኦግራፊ ፒኤችዲያቸው ጋር ተቀበሉ፡፡ « 1978ዓ.ም ለእኔ ልዩ ዓመት ነው፡፡ በአንድ ዓመት ዶክትሬቴን እና የሶስተኛ ዳን ቀበቶዬን የተቀበልኩበት ስኬታማ ዓመት ነው» በማለት ዓመቷን ያወድሷታል፡፡

በዚሀ ብቻ ሳይገደቡ በ1983 ዓ.ም  አራተኛ ዳናቸውን በአሜሪካ ሎሳንጀለስ ተፈትነው ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገበ ተቀበሉ፡፡ ዶክተር ኤልያስ ካራቴ ስፖርትን የሙጢኝ ብለው ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ደግሞ ፈረንሳይ ሀገር አምስተኛ ዳናቸውን በክብር ተቀብለዋል፡፡ በብዙ ሀገራት በርካታ ትምህርት ቤቶችን በመክፈት ባለፉት 50 ዓመታት ከ100 ሺ በላይ ተማሪዎችን ያፈራው የሰንሴይ ኦሺማ ትምህርት ቤት ካሉት  25 ባለሙያዎች አንዱ ናቸው- ዶክተር ኤልያስ፡፡

 ካራቴን ለስራነት

የካራቴ ዳን ከወሰዱ በኋላ በዩኒቨርሲቲዎች እና በተለያዩ ተቋማት በሳምንት እስከ 25 ሰዓት የሚደርስ ስልጠና መስጠት ጀምረው የተሻለ ተከፋይ መሆን ቻሉ፡፡ የካራቴ አሰልጣኝነት እንደ ሌላው ስራ ከባድ እና ዝቅተኛ ክፍያ የሚፈጸምበት አለመሆኑ ረድቷቸው የተሻለ ህይወት መምራት ጀመሩ፡፡የዩኒቨርሲቲው መምህራንን፣ተማሪዎችን እና የፋብሪካ ሰራተኞችን ጭምር እያስከፈሉ ካራቴን ማስተማርን ተያያዙት፡፡

በወቅቱ በፈረንሳይ ውስጥ በየቦታው ካራቴን እየሰሩ ጉዳት የሚያደርሱ ሲበዙ የፈረንሳይ ካራቴ ፌዴሬሽን ማንኛውም ሰው ካራቴ ለማሰራት ፈቃድ ማውጣት እንዳለበት ህግ ወጣ፡፡ ፈተናውንም  ተፈትነው አመርቂ ውጤት በማስመዝገባቸው ፈቃድ አገኙ፡፡

ፈቃዳቸውን ይዘው ማሰልጠኑን የገፉበት ዶክተር ኤልያስ በክልላቸው የመምህራን ማሰልጠኛ ሲከፈት ገብተው እንዲያስተምሩ ተቀጠሩ፡፡በ1984ዓ.ም የማዕከላዊ ክልል ካራቴ ፌዴሬሽን አሰልጣኞች ኃላፊ ሆነው ተሾሙ፡፡ ክልሉን በመወከል በየዓመቱ ፓሪስ እየሄዱ ከሁሉም ክልሎች ከመጡ ባለሙያዎች ጋር ይመካከሩ ጀመር፡፡

   በምክክር መድረኮቹ ላይ ጠንካራ ሀሳቦችን ይሰነዝሩ የነበሩት ዶክተር ኤልያስ ከዓመት በኋላ በፈረንሳይ ካራቴ ፌዴሬሽን ውስጥ በጊዜያዊ ሰራተኛነት ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር ተቀጠሩ፡፡ በየወሩ ከሚኖሩባት ኦርሊንዝ ከተማ ፓሪስ እየተመላለሱ ለአንድ ዓመት ያህል ሰሩ። የፌዴሬሽኑን ስራ ሲያጠናቅቁም አንድ ራሳቸውን የሚያስተዋ ውቁበት መድረክ ተዘጋጀ፡፡ «በትውውቅ መድረኩ ላይ ሁላችንም ከአምስት መስመር በማይበልጥ ሀሳብ ማንነታችንን እንድንገልጽ ጠየቁን፡፡ እኔ ተራዬ ሲደርስ ስሜ ኤሊያስ አቢሻክራ ይባላል፡፡ እድሜዬ 44 ሲሆን በጂኦግራፊ የዶክተሬት ዲግሪ አለኝ ስል ሁሉም ግራ ተጋብቶ ምሁር ነሃ! ብሎ ያደነቀኝን መቼም አልረሳውም» በማለት ዶክተሬታቸው ለሁለተኛ ጊዜ ክብር እንዳጎናጸፋቸው ይናገራሉ፡፡  

     ሌላ እውቀት  ፍለጋ

  መማረን አይጠግቡም፡፡ ዶክተር ኤልያስ በጂኦግራፊ ትምህርት ሳይገደቡ በፓሪስ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሜድሲን ትምህርት መማር ጀመሩ፡፡ሁለት ዓመት ከተማሩ በኋላም አቋረጡ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ቀደም ሲል ዶክተሬታቸውን የተማሩባት ‹‹ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኦርሊንዝ›› የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መክፈቱ ነበር፡፡ በጓደኞቻቸው ግፊት የማስተርስ ዲግሪ በስፖርት ሳይንስ ለመማር ጠየቁ፡፡ አራት ዓመት ከተማሩ በኋላ በስፖርት ሳይንስ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ይዘው ተመረቁ፡፡ ይሁን እንጂ ከማስተርስ ምርቃት በኋላ በ1990ዓ.ም በስፖርት ሳይንስ ፒኤችዲ ዲግሪ እንዲማሩ በጓደኞቻቸው ግፊት ቢያደርባቸውም ለመማር የካራቴ ስራቸውን መተው እንዳለባቸው ስለገባቸው ጥያቄውን ውድቅ አደረጉት፡፡ እርሳቸው ስራቸውን ትተው በሌላ ትምህርት ላይ የሚጠመዱ ከሆነ አዲስ አበባ ውስጥ የሚረዷቸው እናታቸው ችግር ውስጥ እንደሚወድቁ ስለገባቸው እና ለእርሳቸውም ቢሆን ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ላይ እንደሚወድቁ ቁልጭ ብሎ ስለታያቸው ስፖርት ሳይንሱን ሳይማሩ ቀሩ፡፡  

       ወደ ኢትዮጵያ

   ረጅም ዓመት ፈረንሳይ ያሳለፉት ዶክተር ኤልያስ ወጣ ገባ እያሉም ቢሆን ለኢትዮጵያ ካራቴ ስፖርትም ደክመዋል፡፡ ይህንን የተመለከተው የዚያን ጊዜው ስፖርት ኮሚሽን በ2001 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚን በዳይሬክተርነት እንዲመሩ ጥሪ አቀረበላቸው፡፡ዶክተር ኤልያስ ጥሪውን ተቀብለው ጳጉሜ 3ቀን2001ዓ.ም ጓዛቸውን ጠቅልለው ከ37 ዓመታት በኋላ  ከፈረንሳይ አዲስ አበባ ገቡ፡፡ሲመጡ  ግን የዳይሬክተርነቱን ቦታ ሌላ ሰው ይዞት ነበር።እሳቸው ግን የአሰልጣኞች አስተባበሪ ስራ ተሰጥቷቸው ስራቸውን ጀመሩ።በአሁኑ ሰዓት የግላቸው የካራቴ ፕሮጀክት ለማቋቋም በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።

   ቤተሰባዊ ህይወት

   «ለማንም ቢሆን ክብር የምሰጠው በስራው እንጂ በቀለሙ አይደለም» የሚል ጽኑ እምነት ያላቸው ዶክተር ኤልያስ፣ከማንኛውም ሰው ጋር ተግባቢ ቢሆኑም ትዳር ግን አልመሰረቱም፡፡ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ እና አማርኛ ቋንቋን አቀላጥፈው መናገር፣ መጻፍ እና ማንበብ ይችላሉ፡፡ አረብኛ እና ጣሊያንኛ ቋንቋንም በመጠኑ መናገር የሚችሉት ዶክተር ኤልያስ ከጋብቻ ውጭ በልጅነታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እያሉ የወለዷት አንድ ሴት ልጅም አለቻቸው፡፡

  «ፈረንሳይ ሀገር ስኖር አንድ ቀን ወደ ሀገሬ እንደምመለስ ስለማውቅ ትዳር አልመሰረትኩም፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭም የመኖር እና ትዳር የመመስረት ፍላጎት አልነበረኝም፡፡ ፈረንሳይ ውስጥ ልጅ መውለድ ማለት መታሰር ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ትዳር ለመመስረት አንድም ቀን አስቤ አላውቅም» የሚሉት ዶክተር ኤልያስ፣ፈረንሳይ ውስጥ ሲኖሩ ሀኪም ጓደኛ እንደነበረቻቸው እና እርሷም ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት ፍላጎት ስላልነበራት ሳይጋቡ መቅረታቸውን ይናገራሉ፡፡

   የሕይወታቸውን አብዛኛውን ክፍል በመማር እና በካራቴ ስፖርት ያሳለፉት ዶክተር ኤልያስ አሁንም ትምህርትን አይጠግቡም፡፡ ዶክተር ኤልያስ ከዚህ በኋላ ግን ትምህርታቸውን ቆም አድርገው በካራቴ ስፖርት ውስጥ ስኬታማ ጊዜን ማሳለፍ አቅደዋል፡፡

 

ታምራት አበራ

Published in ማህበራዊ

ኢትዮጵያ ፓርላሜንታዊ አስተዳደርን ከሚከተሉ አገሮች መካከል አንዷ ነች።  በዚህ አስተዳደር ስርዓት ሶስት የመንግሥት መዋቅሮች ይገኛሉ። ከነዚህ ውስጥ አንዱና የህግ አውጪ አካል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ምክር ቤቱ በህዝቡ በቀጥታ የተመረጡ ተወካዮችን የያዘ ሲሆን በዋነኝነት ህግ ከማውጣት በዘለለ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ይቆጣጠራል።

ምክር ቤቱ  ህግ የሚያወጣው አዳዲስ ህግጋትን በመደንገግ፣ ነባር ህግጋትን በማሻሻልና በመሻር፣ ዓለም አቀፍ ውሎችንና ስምምነቶችን በማጽደቅ እና የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ  55 ንዑስ ቁጥር 16 እና 18 ላይ ምክር ቤቱ የፌዴራሉን መንግሥት ባለሥልጣናት ለጥያቄ የመጥራትና የሕግ አስፈጻሚውን አካል የመመርመር፣ እንደዚሁም በጉዳዩ ላይ የመመካከርና አስፈላጊ መስሎ የታየውን እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን እንዳለው ተደንግጓል፡፡

የህዝብና የመንግሥት ሀብትና ንብረት በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን፣ ስራዎች ህግና ሥርዓትን መሠረት አድርገው እየተከናወኑ መሆኑን፣ ፍትሃዊና ፈጣን የልማት አቅጣጫ መኖሩን፤ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር መስፈኑ፣ የዜጎች መብት፣ ሠላምና ፀጥታ መከበሩን፣ እንደዚሁም በመንግሥት አካላት መካከል የተቀናጀ አሠራር መኖሩን የማረጋገጥ ስራውን በአግባቡ እየተወጣ አለመሆኑ ይነገራል። ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግሥት አካላትን የመቆጣጠርና የመከታተል ስራውን ዋነኛ አላማ አድርጎ አይንቀሳቀስምም ይባላል።

ምክር ቤቱ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት ላይ የመቆጣጠር ስራ ቢሰራም አጥፍተው ሲገኙ እርምጃ መውሰድ ላይ እንደሚቀረውና በአብዛኛው በአስፈፃሚው አካል ጫና እንደሚደረግበት ይገለፃል። ለህዝቡ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ተቋማት ላይ የሚታየውን የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈታ አለማድረጉ፤ ጥፋት የሚፈፅሙ አስፈፃሚዎችን አለማስቀጣቱና በህገመንግሥቱ የተሰጠውን ስልጣን በአግባቡ አለመጠቀሙ በአብነት ይጠቀሳል። በተለይም በአስፈፃሚው አካል ስልጣኑን በመቀማቱ ሪፖርት ከማዳመጥ የዘለለ ተግባር እንደሌለውም በተደጋጋሚ ይገለፃል። እውን ምክር ቤቱ በተግባር ስልጣኑን በአስፈፃሚው አካል ተቀምቷልን?

የመልካም አስተዳደርና የፀጥታ ጉዳዮች ተመራማሪው አቶ ካህሳይ ገብረእየሱስ እንደሚሉት፤ በህገ መንግሥቱ እንደተቀመጠው ምክር ቤቱ ህግ አውጪ እንደመሆኑ ህግ ያወጣል፡፡ ህግ እንዲተገበር ከማድረግ ባሻገር ህጉ እየተተገበረ መሆኑን ይቆጣጠራል፡፡ ይሄ ማለት አስፈፃሚው ለሚፈፅመው ነገር በህጉ መሰረት ለመፈፀሙ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ምክር ቤቱ ነፃ ሆኖ  ህጉ በሚፈቅደው መሰረት የተቀመጠውን እና የወጣውን ፖሊሲ የማስፈፀም ስልጣንና ሃላፊነት አለው፡፡የመንግሥት አስፈፃሚ አካል ተጠያቂነቱ ለምክር ቤቱ ነው፡፡  ምክር ቤቱም በሙያው ለፖሊሲው ባለው ተልዕኮ ነፃ ሆኖ ሃላፊነቱን ይፈፅማል፡፡ 

የአስፈፃሚው አካልና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንኙነት ህግ የማውጣትና የወጣውን ህግ እንዲተገበር እና ሳይተገበር ሲቀር ተጠያቂ ማድረግ ላይ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ጠያቂው ሲሆን፤ አሁን ባለው ሁኔታ የሁለቱ ስራ የተቀላቀለ ነው የሚሉት አቶ ካሕሳይ፤ የገዢው ፓርቲ አባላት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና አስፈፃሚ አካል በመሆናቸው ህግ የሚያወጣው ገዢው ፓርቲ በተወካዮቹ አማካኝነት ነው፡፡ ተወካዮቹ አስፈፃሚ ሆነው እንደገና በሚኒስቴር ፅህፈት ቤቶች ስራቸውን ሲፈፅሙ ተመልሰው ስራቸውን በሪፖርት የሚያቀርቡት ለምክር ቤቱ ለራሳቸው ስለሆነ በስራ አስፈፃሚውና በምክር ቤቱ መካከል የመጠየቅና የመጠየቅ ስልጣን እንዲላላ ማድረጉንና ስራ አስፈፃሚው አካል በስልጣን መብለጡን  ይናገራሉ፡፡ ‹‹አሁን ባለው ሁኔታ ይሄ በተግባር የሚታይ ነው፡፡ምክር ቤቱ አስፈፃሚ አካላትን  የመጠየቅ አቅሙ ዝቅተኛ ነው ሲባል በህገ መንግሥት የተሰጠውን ስልጣን እየተጠቀመ አይደለም ማለት ነው፡፡ የአስፈፃሚውና የምክር ቤቱ  መቀላቀል የተጠያቂነት አሰራር  እያመነመነ ነው ተብሎ ቢገለፅ የተሻለ ነው››  ይላሉ፡፡ በምሳሌነት በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ ትምህርት ክፍል የተከናወነ ጉዳይ ያነሳሉ፡፡ ትምህርት ክፍሉ የአገሪቱን ህገ መንግሥት የማስተማር ግዴታ አለበት፡፡ አንድ አስተማሪ የአሜሪካን ህገ መንግሥት አስተምሮ የአገሪቱን ህገ መንግሥት የማስተማር  ግዴታ እንዳለበትና  ሳያስተምር ከወጣ  ዩኒቨርስቲው አገሪቱን  እያገለገለ  አለመሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአሜሪካ ህገ መንግሥት ትምህርት ተሰጥቶ የአገሪቱ ህገ መንግሥት ሳይሰጥ የተወጣበት ወቅት እንዳለ የሚናገሩት አቶ ካህሳይ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አካባቢ እና ሌሎች ቦታዎች ላይ የሚያደርገው ቁጥጥር አናሳ መሆኑ አንድ ማሳያ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ህገ መንግሥቱ የህዝቡ ነው፡፡ የአገሪቱ ህዝብ ካላወቀው ትርፍ ተቀማጭ ንብረት አይደለምና ይህን ከማስፈፀም አንፃር ትልቅ ስራ ምክር ቤቱ እንደሚጠብቅበት ያስረዳሉ፡፡

 በሌላ በኩል በህገ መንግሥቱ እንደተቀመጠው የንብረት ባለቤትነት መብት የሁሉም ዜጋ ነው፡፡ በህጉ መሰረት ንብረት መሸጥና መግዛት ይቻላል፡፡ በአንዳንድ የክልል ከተሞች ነፃ ገበያው ተጥሶ ለታክስ ሲባል የመንግሥት ሰራተኞች ኪራይ የሚተምኑበት አሰራር ተጀምሮ እንደነበርና በአሁን ሰዓት ችግር በመፍጠሩ መቆሙን ይጠቅሳሉ። ምክር ቤቱ ህገመንግሥቱ የሚተገበርበት በመሆኑ ሁሉም ነገሮች ላይ በስነስርዓት መከታተል ካልቻለ፤ ያወጣው ህግ ወደ ተግባር የማይለወጥ ከሆነ፤ እንደእነዚህ አይነት ሁኔታዎች ሲበዙ የፖለቲካ ስርዓቱና ህገ መንግሥቱ  አደጋ ላይ  የሚወድቁበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ያብራራሉ፡፡

 ምክር ቤቱ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት የሚጠበቅበት በአግባቡ ክትትል ማድረግና ሪፖርት የሚያዳምጥበትን መንገድ በመለወጥ የሚቀርቡ ሪፖርቶች አስፈፃሚ አካላትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ እንዲሆኑ መስራት አለበት። ለምሳሌ  ያልተተከለ ተክል ተተክሏል ተብሎ ሪፖርት ሲቀርብ  በአካል ሲኬድ ሊገኝ የሚችል መሆን እንዳለበት ያስቀምጣሉ። በአስፈፃሚው የሚቀርቡት ሪፖርቶች ተመልሶ ማረጋገጥ ይቻላል ወይ ተብሎ የማረጋገጥና የመፈተሽ ስራ የምክር ቤቱ ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ህገ መንግሥቱ የሰጣቸውን መብቶች እንዳይሸራረፉ በአስፈፃሚ በኩል የሚሰሩ ስራዎች የመከታተያ አሰራሮች ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌዴራሊዝም መምህር አቶ ናሁሰናይ በላይ እንደሚናገሩት፤ በህገ መንግሥቱ እንደተቀመጠው የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ናቸው፡፡ ይሄ የሚገለፀው የኢትዮጵያ ህዝብ በሚያደርገው ምርጫ ተወካዮቹን መርጦ ተወካዮቹም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገብተው የህዝቡን ድምፅ ሲያሰሙ ነው፡፡ በተጨማሪም የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ላይ ቁጥጥር ሲያደርጉ ውክልናው ተገቢና ትክክል ከመሆን ባሻገር የምክር ቤቱ አባላትም ሃላፊነታቸውን የሚወጡበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ሆኖም ህገ መንግሥቱ ካስቀመጠው አንፃር  በተግባር ሲታይ አስፈፃሚው አካል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን  እየተቆጣጠረ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሥራው መገልበጡን ያሳያል፡፡

አቶ ናሁሰናይ ለችግሩ በመጀመሪያ ምክንያትነት የሚያስቀምጡት ገዢው ፓርቲ  በማዕከላዊ ኮሚቴ ማለትም በፓርቲ ምክር ቤት ወይም በስራ አስፈፃሚው የተወሰነውን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመንግሥት ተወካይ አማካኝነት ይቀርባል፡፡ በምክር ቤቱ ውስጥ ያሉ ተመራጮች ጉዳዩን በአግባቡ ሳይመረምሩ  የመንግሥት ተጠሪውን ተከትለው  ድምፃቸውን ስለሚሰጡ ነው ይላሉ።

 በመርህ ደረጃ  ምክር ቤት ውስጥ የሚገቡ ተወካዮች ተጠሪነታቸው ለመረጣቸው ህዝብ፣ ለህሊናቸውና ለህገመንግሥቱ ነው፡፡  አሁን ባለው አሰራር ተወካዮቹ  ተጠሪነታቸው  ለመጡበት ፓርቲ በመሆኑ ችግሩ እንዲፈጠር ማድረጉን ይጠቅሳሉ፡፡ የፓርቲው ፖለቲካዊ ባህል የተዛባ በመሆኑ  የውሳኔ አሰጣጥ ዘይቤው በራሱ በሥራ አስፈፃሚው ሥራዎች ስለሚያልቁ ጉዳዩ ወደ ምክር ቤት ሲሄድ በትክክል ውይይት አይካሄድበትም፡፡ ይሄ የሚያሳየው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚጠበቅባቸው  የመጣውን ውሳኔ ተቀብለው ማፅደቅ ብቻ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡

 ህገ መንግሥቱ በስርዓቱ ባለመተግበሩ የስራ አስፈፃሚው ጉልበት በግልፅ የጎላ  እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ስለዚህ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአግባቡ ሥራውን ማከናወን አልቻለም፡፡ሥራውን በአግባቡ መወጣት ያቃተው ምክር ቤቱ ብቻ አይደለም፡፡ ፍርድቤቱም የስራ አስፈፃሚው ተከታይ በመሆኑ ሥራ አስፈፃሚው በፍርድ ቤቱም ላይ ያልተገባ ጉልበትና ቁጥጥር  እያደረገ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡ 

   ባለፈው ዓመት በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ችግሮች ተፈጥረው ነበር። የችግሮቹ ምንጭ ግለሰቦች ስልጣን የመፈለግ እና በስልጣን የመጠቀም አዝማሚያ ስላላቸው ነው የሚል በጣም የተሳሳተ ድምዳሜ ተይዟል የሚሉት አቶ ናሁሰናይ፤ በአሁን ሰዓት ያለው የመንግሥት የስልጣን ስርዓት ስልጣንን ለግል ጥቅም ከማዋል ወደ ብዝበዛ የሚገፋ ባህሪ ስላለው  ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡

የፖለቲካ ምሁራን  የመንግሥት ስልጣን  ህዝቡን መበዝበዣ  እንዳይሆን ልጓም ይቀመጥለት  የሚል አቋም እንዳላቸው ገልፀው፤ ለእዚህም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፖለቲካል ፓርቲዎች መጠናከር እና መገናኛ ብዙኃኑ ነፃ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ  ማድረግ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ያስረዳሉ። 

  ‹‹ሰዎች መላዕክት አይደሉም  መላዕክት ቢሆኑ መንግሥት ባላስፈለጋቸው ወይም መንግሥት የሚሆነው ሰው የመላዕክት ስብስብ ቢሆን ቁጥጥር ባላስፈለገው ነበር›› የሚሉት አቶ ናሁሰናይ፤ አሁን ያለው መንግስት  በሰዎች የተመሰረተና በሰዎች ላይ የሚሰራ በመሆኑ ስልጣንን ለግል  ጥቅም የማዋል ዝንባሌ ሊኖር ይችላል። ይሄን ለማስተካከልና ለመቀነስ  ሰዎችን መቀያየር መፍትሄ  እንደማይሆንና ዋናው መፍትሄ መዋቅራዊ የቁጥጥር ስርዓት ማበጀት እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ በምሳሌነትም ስራ አስፈፃሚው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ በተለያየ መንገድ  ቁጥጥር ማድረግ ሲቻል መሆኑን ያነሳሉ፡፡

ስልጣን ለግል ጥቅም እንዳይውል  ፍርድ ቤቶች ፍርድ ቤት እንዲሆኑ እና ተገቢውን ሚና እንዲወጡ በማድረግ እንዲሁም ፍርድ ቤቶች ከአላስፈላጊ ተፅዕኖ ማለትም ከባለስልጣን ማስፈራራት፣ ከሹመት ማውረድ፣ በስራ አስፈፃሚው ከመገምገም ነፃ መሆን እንዳለባቸው ያብራራሉ፡፡ መንግሥት ፍርድ ቤትን እና የተወካዮች ምክር ቤትን እየረገጠ የሚይዝ ከሆነ ከባድ ስለሚሆን  ህገ መንግሥቱን  ህይወት እንዲኖረው በማድረግ ለውጥ ለማምጣት እንቅስቃሴ መጀመር እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡

 አሜሪካኖች ህገ መንግሥታቸውን ሰርተው በጨረሱበት ወቅት ከህዝቡ ይሄ ህገ መንግሥት የተሰራው ንጉሳዊ ቤተሰብ ለሆኑት ነው?  ወይስ በህዝብ ለሚመረጥ መንግሥት ነው  የሚል ጥያቄ ሲቀርብላቸው፤ ህገ መንግሥት ወረቀት ላይ ያለ ነገር ነው፡፡ ህገ መንግሥቱ ትርጉም የሚኖረው ህዝቡ ሕይወት ላይ  ሲንፀባረቅ ነው የሚል ምላሽ እንደሰጡ በአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ በጣም ጥሩ ህገ መንግሥት አላት።ህገ መንግሥቱ በአሰራርም በይዘትም አገራዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያስችላል፡፡ ነገር ግን ተግባራዊ መሆን አለበት ሲባል ስራ አስፈፃሚው ቁጥጥር ያስፈልገዋል፡፡ በግለሰብ የሚወሰኑ ውሳኔዎች በማስቀረት መዋቅራዊ ቁጥጥር በመፍጠር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆኑን ይገልፃሉ፡፡

 ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በፌዴራሊዝምና በመንግሥት አስተዳደር የሰሩት አቶ ዝናቡ ይርጋ እንደሚያብራሩት፤ ኢትዮጵያ የፓርላማ ስርዓት ከሚከተሉ አገሮች መካከል አንዷ ነች፡፡ በህገ መንግሥቱ እንደተቀመጠው  ህዝብ ሉአላዊ የስልጣን ባለቤት ነው፡፡ ህዝቡ ስልጣኑን ለመጠቀም እና መብቱን ለመግለፅ በቀጥታ የሚወክለውን በመምረጥ ወደ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይልካል፡፡ ከህዝብ የተወከለው የስልጣን ባለቤት በመሆኑ በመንግሥት መዋቅሮች ማለትም ከስራ አስፈፃሚ እና ከፍርድ ቤት በፊት ባለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆኑን ህጎች እንዲወጡ ያደርጋል ፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ምክር ቤቱ የተሰጠውን ስልጣን በአግባቡ እየተጠቀመበት ነው ወይ? ለሚለው ጥያቄ በመጀመሪያ በህገመንግሥቱ  አንቀፅ 55 ላይ  የተዘረዘሩትን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስልጣን ሲታይ በተለይ ስራ አስፈፃሚዎችን የመቆጣጠር ስራውን በአግባቡ እየተወጣ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህዝቡ የሰጠውን ስራ አስፈፃሚውን የመከታተል የመቆጣጠር፣ የማስተካከልና የማረም ስራ በአግባቡ ባለመወጣቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህዝቡ ሉአላዊ መገለጫ የሆነውን ስልጣን  በአግባቡ እየተጠቀመበት አለመሆኑንም ያነሳሉ፡፡

በአገሪቱ የስልጣን ደረጃ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛው ነው፡፡ በዋናነት ስራ አስፈፃሚውን የመከታተል ግዴታም አለበት፡፡ ክፍተቶች ሲኖሩ አስፈፃሚዎችን ከስልጣን ያነሳል፡፡ በመንግሥት ሹመት ይቅረብለት እንጂ የማፀደቅ ስራው የምክር ቤቱ ነው፡፡ እስካሁን ያሉት ነገሮች ሲታዩ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ ጥሩ ነገሮች ተፈጥረዋል፡፡ በዛው ልክ በተለይ ከአቅም ማነስ እና ከአመለካከት ችግር ጋር የሚመጡ ችግሮችም ተስተውለዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ከማየትና ከማስተካከል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድርሻ አነስተኛ ነበር፡፡ ለእዚህም ዋናው ምክንያት ሪፖርት ከማድመጥ ባለፈ ሪፖርቱን ተከትሎ የተሰራ ስራ ባለመኖሩ የህዝብ ወኪል ሆኖ የተሰጠውን አደራ የተወጣና እየተወጣ ያለ ተቋም አይደለም የሚል እምነት እንዳላቸውም ያስረዳሉ፡፡  

ስራ አስፈፃሚው ከምክር ቤቱ የበለጠ ስልጣን አለው የሚባለው አስተያየት ትክክል መሆኑንና  በአሁን ወቅት ስራ አስፈፃሚው ከምክር ቤቱ ይቅርና ከፍርድ ቤቱ በላይ የሆነ ስልጣን እንዳለው በመጠቆም፤ በመርህ ደረጃ ያለው ሶስቱ የመንግስት መዋቅሮች ህግ አውጭው፣ ህግ ተርጓሚውና ህግ አስፈፃሚው እርስ በራሳቸው ቁጥጥር የሚያደርጉበት መንገድ ያለ ቢሆንም በተግባር ሲታይ የስራ አስፈፃሚው ስልጣን ከፍተኛ ሆኖ ይታያል ይላሉ፡፡ ስለዚህ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህገ መንግስቱ  በፅሁፍ የተቀመጠለት ኃላፊነት  በተግባር የሰራው ነገር የለም፡፡

ምክር ቤቱ የተሰጠውን ስልጣን በአግባቡ እንዲጠቀም የአመራር ስራው ሙያዊ መሆን አለበት፡፡ በህገ መንግስቱ የተሰጠው ስልጣን ከፍተኛ ቢሆንም አሁን ያለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሲታዩ   ውጤት የሚያመጡ አይደሉም፡፡ ህግ የማውጣት ስልጣን የነሱ በመሆኑ በመጀመሪያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መሆን ያለባቸው ሰዎች ሙያዊ ክህሎት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሁለተኛው ስራ አስፈፃሚውን ለመከታተል አቅምና እውቀት ሊኖር እንደሚገባ ያብራራሉ፡፡ ስራ አስፈፃሚው የተለያዩ ስራዎች እንዲሰራ የተሾመ አካል በመሆኑ ያንን አስፈፃሚ ለመከታተል  የካበተ እውቀት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ እውቀትና ክህሎት የሌለውን ሰው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆኑ ብቻ አስፈፃሚውን እንዲከታተል ማድረግ ውጤት አያመጣም፡፡  በግለሰብ ደረጃ  ሲታይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአባል አቅም ከስራ አስፈፃሚው ያነሰ በመሆኑ  አስፈፃሚውን በሙሉ አቅም መቆጣጠር እንዲሳናቸው ማድረጉን ያስረዳሉ፡፡

በመጀመሪያ የህዝብ ተወካዮቹ ሲመረጡ አቅማቸውና እውቀታቸው ከዛም የድርጅቱ አባላት መሆን ስለሚገባቸው ያላቸው አመለካከት በአገሪቱ የእድገት ስራዎች ላይ የሚያደርጉት አስተዋፅኦ በመስፈርትነት መቀመጥ አለበት፡፡ ክህሎቱና እውቀቱ ግን ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ሌላው ህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን ግዴታ መፈፀም ሲሆን  የህግ እውቀታቸው ከፍ ያለና ለዛ ተገዢ መሆን አለባቸው፡፡ በሌላ በኩልም የህዝብ ቀጥተኛ ወኪል በመሆናቸው ህዝብ ካልፈለጋቸው እንደሚያወር ዳቸው በመረዳት ህዝብ ሉአላዊ የስልጣን ባለቤት መሆኑ ሊያምኑ ይገባል፡፡ ተመርጠው ከመጡ በኋላ ህዝቡን ሊረሱት አይገባም ምክንያቱም አንዳንዶች የመረጣቸውን ህዝብ ወደ ጎን በመተው የራሳቸውን ኑሮ ሲያመቻቹ እንደሚስተዋል ይናገራሉ፡፡

 

መርድ ክፍሉ

Published in ፖለቲካ

በአገሪቱ የተፈጥሮ ምንጭ ውሃና የተፈጥሮ ማዕድን ውሃ አምራች ድርጅቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየተበራከተ መጥቷል፡፡ ከስራ እድል ፈጠራ ጀምሮ ለኢኮኖሚው የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ እነዚህ ምርቶች የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው ለገበያ ካልቀረቡ ግን በህብረተሰብ ጤና ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት በቀላሉ የሚገመት እንዳልሆነ ክርክር አያሻውም፡፡

    አለም ዓቀፍ ተሞክሮዎችን መሰረት በማድረግ እ.ኤ.አ በ2013 በአገር ውስጥ የሚመረቱና ከውጭ አገራት የሚገቡ ምርቶችን ጥራት የመለኪያ ደረጃ ተዘጋጅቷል፡፡ አስገዳጅና አስገዳጅ ያልሆኑ የጥራት ደረጃ አሰጣጥ ስርዓትም ተዘርግቷል፡፡ የአገሪቱ አስገዳጅነት ደረጃ መስፈርት ከምርት ሂደት እስከ አስተሻሸግና የመለያ ምርት ስያሜ ድረስ ሊሟሉ የሚገባቸውን የጥራት ሂደቶች ያካትታል፡፡ አስገዳጅ ያልሆኑ ደረጃዎች ድርጅቶች ሳይገደዱ በፍላጎታቸዉ የሚያሟሉት ደረጃ ነው፡፡

   የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ይስማ ጅሩ መንግሥት አጣርቶ ለህብረተሰቡ የሚያሰራ ጨውን የመጠጥ ውሃ ጨምሮ የታሸገ ውሃና በተፈጥሮ ማዕድን የበለፀገ ውሃ አመራረት ጥራትን የሚወስን  መስፈርት በስራ ላይ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡

   «ደረጃቸው በቴክኒክ ኮሚቴ አርቃቂነትና በብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት አፅዳቂነት መስፈርቱ  ረቆና ፀድቆ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ የውሃ ምርት በአስገዳጅነት ደረጃ የሚገኝ ነው፡፡ የአስገዳጅነት ደረጃ ማለት ምርቶች የግድ ሊያሟሉዋቸው የሚገቡ መስፈርቶች የያዘ ሰነድ ነው፡፡ከጤና፤ ከደህንነት፤ ከአካባቢ ጥበቃ፤ ከአሳሳችነት ተግባርና ከአገር ብሄራዊ ደህንነት አንጻር ከጥራት በታች ሆነው ሲገኙ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ምርቶች በአስገዳጅ ደረጃ እንዲያልፉ ይደረጋል›› ይላሉ፡፡

  አቶ ይስማ እንደሚገልፁት፤አስገዳጅ ያልሆኑ ደረጃዎች ድርጅቶች ሳይገደዱ የሚያሟሉት ደረጃ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል የስራ አመራር  ስርዓት አንዱ ነው፡፡ ይህ አሰራር የደንበኛን እርካታ ማረጋገጥ  ዋነኛ ግቡ ይሆናል፡፡ የስራ አመራር ስርዓቱ ደረጃውን የጠበቀ ከሆነ ጥራት ያለው ምርት ለማምረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ እናም ተቋማቱ ደረጃቸው ሲጣራ አስገዳጁ ምርታቸው ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ አስገዳጅ ያልሆነው ደግሞ የአመራረት ሂደታቸው ላይ ነው፡፡

  ከዚህ አንፃር የታሸጉ ውሃዎች የጥራት መስፈርታቸው ሲታይ በተፈጥሮ ማዕድን የበለፀገ ውሃ የአስገዳጅነት ጥራት ደረጃ የተለያየ ነው፡፡ የአገሪቱ የአስገዳጅነት ደረጃ መስፈርት  ከምርት ሂደት እስከ አስተሻሸግና የመለያ ምርት ስያሜ ድረስ ሊሟላ የሚገባውን ጉዳይን ያካትታል፡፡ አንድ የታሸገ ውሃ ሊያሟላቸዉ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁ መስፈርቶች መካከል የማግኒዝየም፤ ካልሺየም፤ ሶዲየም፤ ፖታሺየም ክሎራይድ፤ ባይካርቦኔትና ሌሎች መዓድኖች መጠን የተወሰነ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይህኛው መዓድን መጠኑ ይህ ነው፣ሌላኛዉ ከዚህ በታች ይሁን ማለት ባይቻልም ለቅመማ በሚመቻቸው መንገድ ከተቀመጠው ምጣኔ ከፍና ዝቅ እንዳይል የምጣኔ ገደብ ተቀምጧል፡፡በተቀመጠው ገደብ መካከል መንቀሳቀስ ይችላሉ በማለት የጥራት ደረጃዎቹን መስፈርቶች ያስረዳሉ፡፡

  ኤጀንሲዉ ፈቃድ ከመስጠት በዘለለ የቁጥጥር ሚናው ዘለግ ያለ መሆኑን እና ቅንጅታዊ አሰራርን በመከተል ከሚመለከታቸው  አካላት ጋር እንደሚሰራም ይናገራሉ፡፡ለኤጀንሲው ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ደረጃውን ጠብቀው ምርታቸውን ለገበያ ለማቅረብ ሃምሳ ሶስት የታሸገ ውሃ ምርትና ሰባት የታሸገ የተፈጥሮ ሚነራል ውሃ አምራቾች እንደየተሰማሩበት ዘርፍ ፈቃድ ወስደዋል፡፡በገበያ ላይ ደረጃውን የጠበቁ ምርቶች እየተሰራጩ እንደሆነ ለማረጋገጥ የክትትል ስራ በባለስልጣኑ እንደሚከናወን አቶ ይስማ ይገልፃሉ፡፡

  የቁጥጥርና ክትትል ስራው ቅንጅታዊነት በተሻለ ደረጃ እንደሚገኝ እና ድርጅቶቹን የመቆጣጠር ሂደቱ ከገበያ ጀምሮ እስከ ምርት ሂደታቸው የዘለቀ በመሆኑ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ምርቶች እንዳይኖሩ ቁጥጥሩ መጠናከሩን ያሰምሩበታል፡፡

  የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት አምራቾች ምርታቸው ደረጃውን የጠበቀ መሆንን በመመርመር የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬትን በመስጠት የደረጃ ማረጋገጫ ምልክቱን እንዲጠቀሙ ፈቃድ እንደሚሰጥ ይታወቃል፡፡ የድርጅቱ የማርኬቲንግና ኮርፖሬት ኮሙንኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተክኤ ብርሃነ ቁጥራቸው ሃምሳ የሚጠጉ መስፈርቶች  የታሸጉ ውሃ ምርቶችን ጥራት ማረጋገጫነት ይውላሉ በማለት፤ ይህን ተከትሎ ለስልሳ የተፈጥሮ ምንጭ ውሃና የተፈጥሮ መዓድን ውሃ አምራች ድርጅቶች የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት መሰጠቱን ይናገራሉ፡፡ በውሃዎች ጥራት ላይ ከሚከናወኑት ፍተሻዎች መካከል የፊዚካል፤ ኬሚካል፤ ማይክሮ ባይሎጂ እና ሌሎች አስገዳጅ ደረጃዎችን አሟልተው ሲገኙ እውቅና እንደሚሰጣቸዉ ይገልፃሉ፡፡

  በመጀመሪያ የምርት ሂደት ጥራት ያላቸውና ለህብረተሰቡ ጤና ተስማሚ መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ ከተቀመጠው የጥራት ደረጃ በታች የሆነ የታሸገ ውሃ ምርት ሲያጋጥም ከንግድ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒት እና የጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በመሆን ምርቶቹ እንዲሰበሰቡና እርምጃ እንዲወሰድባቸው የማድረግ ስራ እንደሚሰራ ነው አቶ ተክኤ የሚያስረዱት፡፡      ነገር ግን ንግድ ሚኒስቴር በሚወስዳቸው እርምጃዎች ላይ ምን ያህል ቁርጠኛ መሆኑን እና ችግሩን ለመፍታት የሄደበትን መንገድ እንደማያውቁት ይናገራሉ፡፡ 

    የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒት እና የጤና ክብካቤ አስተዳደር የምግብ አምራቾች ኢንስፔክሽን ቡድን መሪ አቶ ገረመው ጣሰው፤ ጥራት ላይ በአጠቃላይ ውሃና ምግቦች ላይ ልዩ ትኩረት ይደረጋል ይላሉ፡፡ የውሃ ድርጅቶችን በመለየት የኢትዮጵያ አስገዳጅ ደረጃዎችን መሰረት በማድረግ ልዩ የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱንም ይናገራሉ፡፡ “የታሸገ ውሃ አምራች ድርጅት የአገሪቱን የውሃ ጥራት ደረጃ ሳያሟላ ወደ ምርትና ወደ ገበያ እንዲገቡ አይፈቀድም፡፡ በመሃል ችግር ሲያጋጥም ድርጅቶቹ ምርት እንዳያመርቱና ካመረቱና ካሰራጩም ምርታቸውን ከገበያ እንዲሰበስቡ ይደረጋል ይላሉ፡፡

   በ2009ዓ.ም በጀት ዓመት የስድስት ወር ዕቅድ አፈፃጸም መሰረት የተፈጥሮ ምንጭ ውሃና የተፈጥሮ መዓድን ውሃ አምራች ድርጅቶች ላይ በተደረገ ምርመራ ሶስት ፋብሪካዎች ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው ሁለት የታሸገ ውሃ ፋብሪካዎች ምርት እንዳያመርቱ እገዳ እንደተጣለባቸው ነው የሚናገሩት፡፡

   በአሁኑ ወቅት በሚከተሉት የአመራረት ሂደት ወደፊት ለውሃ ምርት ጥራት ስጋት ይሆናሉ የተባሉ ሶስት ድርጅቶች አመራረታቸውን በጥራት እንዲተገብሩ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት መገደዳ ቸውን አቶ ገረመው ይገልፃሉ፡፡ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ድርጅቶች ለተወሰነ ጊዜ ምርታቸውን ወደ ገበያ ሳያስገቡ  ጥራቱን በማስተካከል ምርታቸውን ለገበያ ማቅረብ የሚችሉ መሆኑንም ያስታውሳሉ፡፡ ነገር ግን የምርታቸው ጥራት ለሰዎች ጤና ስጋት በሚሆንበት የጥራት ደረጃ ላይ የሚገኙ ድርጅቶች እገዳ ይጣልባቸዋል ይላሉ፡፡

   ስርዓቱን ጠብቀው ምርታቸውን በማስፈተሸ ለገበያ የሚያቀርቡ ድርጅቶች እንዳሉ ሁሉ አንዳንዶቹ ምርታቸው በምርመራ ሂደት ሳያልፍ በቀጥታ ወደ ገበያ ሲያሰራጩ የምርት ጥራት ችግር ያጋጥማል ይባላል በሚል ለቀረበላቸው ሃሳብ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ  የቁጥጥር ሂደት ከገበያ ቅኝት ስለሚጀምር ከቁጥጥር የማምለጥ እድሉ የተመናመነ መሆኑን አቶ ገረመው ይናገራሉ፡፡

   “ያልተፈተሹና የማይታወቁ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያልተመዘገቡና የተስማሚነት ምዘና ሰርተፊኬት የሌላቸው የታሸጉ ውሃ ምርቶች በቅድሚያ ከገበያ ተሰብስበው በላብራቶሪ ጥራታቸው ተረጋግጦ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆነው ከተገኙ ከገበያ መሰብሰባቸው እንደ ቅጣት ይቆጠርና ምርቱ ይቀጥላል፡፡ ጥራታቸው ካልተጠበቀ እና የታሸገ ውሃ ምርት ከተቀመጠው ደረጃ በታች ሆኖ ሲገኝ እግድ ይጣልበታል” ሲሉ ይናገራሉ፡፡

   ከጥራት በታች የሆኑ ምርቶችን ከገበያ በመሰብሰብ እንዲወገዱ የማድረግ ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉን የሚናገረዉ የቡድን መሪው፤ የህብረተሰቡ ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡

ጤናማ የንግድና ኢንዱስትሪ ስርዓት የሚገነባዉ ጤናማ ህብረተሰብ መፍጠር ሲቻል ነው፡፡ በተቀናጀ አሰራር ለህብረተሰቡ ጤና ስጋት የሆኑ የታሸጉ ውሃ ምርቶች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ለይደር የሚተው ጉዳይ አይሆንም ብለውናል፡፡ ይህን ዘገባ ለማጠናቀር  የንግድ ሚኒስቴርን ለማነጋገር ያደረግነዉ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

 

ራጁ መሃመድ

Published in ኢኮኖሚ

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

 

የበርካቶችን ግምትና መላምት ፉርሽ አድርገው የልዕለ ኃያሏ አገር፣ የአሜሪካ 45ኛው ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት ቢሊየነሩ ዶናልድ ጆን ትራምፕ፣ በነጩ ቤት መንበር ላይ ከተቀመጡ 15 ቀናት እንኳ ሳይሞላቸው የወሰኗቸው ውሳኔዎችና ያስተላለፏቸው ትዕዛዞች በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ቁጣን እንዲሁም ግርምትን ፈጥረዋል፡፡ አሜሪካን በደቡብ በኩል በምታዋስናት ሜክሲኮ ድንበር ላይ አጥር እንዲገነባ፣ ለበርካታ አሜሪካውያን የጤና መድኅን ሽፋን የሚሰጠው መርሃ ግብር (Obama care) እንዲሻር እንዲሁም በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻቸው ወቅት ለደጋፊዎቻቸው ቃል የገቧቸውን ዕቅዶች ያሳኩልኛል ያሏቸውን ውሳኔዎች እየወሰኑ ይገኛሉ፡፡

  ፕሬዚዳንቱ እስካሁን ይፋ ካደረጓቸው የውሳኔ ሃሳቦቻቸው መካከል እ.አ.አ ጥር 27 ቀን 2017 ያሳለፉት ውሳኔ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለየት ያለና የበረታ ተቃውሞን አስከትሎባቸዋል፡፡ ውሳኔው የሰባት አገራት ማለትም የኢራን፣ ኢራቅ፣ የመን፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ሶርያና ሊቢያ ዜጎች ውሳኔው ከተላለፈበት ዕለት ጀምሮ ባሉት 90 ቀናት ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ እገዳ የሚጥል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የማንኛውም ሃገር ስደተኞች ከውሳኔው ዕለት ጀምሮ ባሉት 120 ቀናት ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚከለክል ይዘትም በውሳኔው ውስጥ ተካትቷል፡፡ 

ታዲያ ይህን የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ ተከትሎ አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ትልልቅ ከተሞች ውሳኔውን የሚያወግዙ ትልልቅ የተቃውሞ ሰልፎችን አስተናግደዋል፡፡ ለወትሮውም ቢሆን በአወዛጋቢነታቸው የሚታወቁት ትራምፕ የሰሞኑ ውሳኔያቸው ደግሞ ከወዳጆቻቸው ሳይቀር ተቃውሞን አስከትሎባቸዋል፡፡

   የተለያዩ አገራት መሪዎችና ታዋቂ ሰዎች (የትልልቅ ኩባንያዎች ስራ አስፈፃሚዎች ሳይቀሩ) እንዲሁም ፖለቲከኞችም በፕሬዚዳንቱ ውሳኔ የተሰማቸውን ስሜት ማኅበራዊ ድረገፆችን ጨምሮ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡ 

   ቀድሞውንም ቢሆን በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የሰፋ የፖለቲካ ልዩነት ያላቸው የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ከውሳኔው በኋላ ተቃውሟቸውን ለመግለፅ የቀደማቸው አልነበረም፡፡ ለአብነት ያህል፣ የዴሞክራቲክ ፓርቲ የኒውዮርክ ሴናተር ቸክ ሹመር በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሑፍ “የአሜሪካ የነፃነት ሀውልት እንባ ሲያነባ ይታያል” በማለት ውሳኔውን ተቃውመዋል፡፡

   ነጩን ቤት ከለቀቁ አንድ ወር ያልሞላቸው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ “ሰዎችን ኃይማኖታቸውን መሰረት አድርጎ ማግለል ፍፁም ተቀባይነት የለውም፤ በተቃውሞ ሰልፎቹ ልቤ ተነክቷል” በማለት ለወትሮውም ቢሆን በሃሳብ የማይስማሟቸውን አልጋ ወራሻቸውን ተቃውመዋል፡፡

ሌላው የዴሞክራቲክ ፓርቲ ሴናተር ኤድዋርድ ማርኪ ውሳኔው ከልክ ያለፈ መጤ ጠልነትን (Extreme Xenophobia) የሚያስፋፋ እርምጃ በመሆኑ የአገሪቱን ክብር የሚያኮስስ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ተቃውሞው ከአሜሪካ ምድር ተሻግሮ አውሮፓንና እስያንም አዳርሷል፡፡ 

  የአውሮፓ ኅብረት ኃያላኑ ጀርመንና ፈረንሳይም በመሪዎቻቸው በኩል በፕሬዚዳንቱ ውሳኔ መከፋታቸውን አስታውቀዋል፡፡ አገራቸውና ህዝባቸው ብቻ ሳይሆኑ መላ አውሮፓውያን ለስደተኞች ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያደርጉ በፅኑ አቋማቸውና በተግባራቸው የሚታወቁት የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል፣ ውሳኔው በምንም ዓይነት መልኩ ተቀባይነት እንደሌለውና ዓለም አቀፉን የሥደተኞች መብት እንደሚጥስ ተናግረዋል፡፡

   የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ በበኩላቸው፣ “አክራሪነትንና መነጠልን የሚያበረታቱ ፖሊሲዎችን በፅኑ ልናወግዝ ይገባል” በማለት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ብቻ ሳይሆን “የአውሮፓ ኅብረት በማስቀምጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ካልተስማማ ፕሬዚዳንት ሆኜ በተመረጥኩ ማግሥት ፈረንሳይን ከአውሮፓ ኅብረት አስወጣታለሁ” የሚሉትን የፈረንሳይ ብሔራዊ ግንባር (France National Front) መሪና ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ማሪን ለ ፐንን በነገር ሸንቆጥ አድርገዋቸዋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም፣ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም ጀርመንና ፈረንሳይ የፕሬዚዳንት ትራምፕን ውሳኔ አጥብቀው እንደሚቃወሙ አረጋግጠዋል፡፡

   የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲግማር ጋብርኤል፣ “አሜሪካ ለክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ ትልቅ ቦታና ወሳኝ ሚና የምትሰጥ አገር ናት፤ ሰዎችን መውደድና መርዳት ደግሞ ከሃይማኖቱ መርሆች አንዱ ነው፤ ምዕራባውያንን አንድ የሚያደርገን ይህ መመሪያና ተግባር ነው፤ ለአሜሪካውያን ግልፅ እንዲሆንላቸው የምንፈልገውም ይኸው ነው” ሲሉ፣የፈረንሳይ አቻቸው ዥያን-ማርክ አይሮል በበኩላቸው፣ «ጭቆናንና ጦርነትን የሚሸሹ ስደተኞችን መቀበልና ማስተናገድ ኃላፊነታችን ነው» በማለት የዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ ሃይማኖታዊ አስተምህሮንም የሚፃረር ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡ 

  ከኅብረት ይልቅ መነጠልን በማቀንቀን ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ተመሳሳይ አቋም ያላቸው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ትሬዛ ሜይ እንኳ በውሳኔው እንደማይስማሙና መሰል ሃሳብ አማራጭ እንደማያደርጉ ገልፀዋል፡፡         

   የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ የዶናልድ ትራምፕን ስምና ውሳኔ ሳይጠቅሱ “ከጦርነትና ሽብርተኝነት ለማምለጥ አገራችሁን ጥላችሁ ለምትሰደዱ ሁሉ ካናዳውያን በራችን ክፍት ነው፤ ልዩነት ጥንካሬያችን ነው” በማለት ባስተላለፉት መልዕክት ከፕሬዚዳንቱ ውሳኔ በተቃራኒ ወገን መቆማቸውን አሳይተዋል፡፡    

     ከ1979ኙ እስላማዊ አብዮት ወዲህ ከአሜሪካ ጋር የማትጣጣመው ኢራን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ መሃመድ ጃቫድ ዛሪፍ በኩል ለውሳኔው ያላትን ተቃውሞ ለማሰማት ጊዜ አልፈጀባትም፡፡ ሚኒስትሩ በትዊተር ገፃቸው ላይ “ከሙስሊም አገራት የሚመጡ ዜጎችን ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ መከልከል ለአክራሪዎችና አሸባሪዎች እንዲሁም ለደጋፊዎቻቸው ትልቅ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ታሪካዊ ስህተት ነው፤ እገዳው አሜሪካ ከኢራን ጋር አለኝ የምትለው ግንኙነት መሰረተ-ቢስና የውሸት እንደሆነ በግልፅ ያሳያል፤ ለሽብርተኝነት መፍትሄ ለመሻት ዓለም አቀፍ ውይይትና ትብብር እንጂ የዜጎችን እንቅስቃሴ መከልከል አማራጭ አይሆንም” በማለት ጽፈዋል፡፡    

  ከምርጫ ቅስቀሳቸው ጀምረው በአሜሪካና በሜክሲኮ ድንበር ላይ ግንብ እገነባለሁ ሲሉ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ፣ የፕሬዚዳንትነት ስልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ ይህን ሃሳብ ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችላቸውን ውሳኔም ማስተላለፋቸው የሚታወስ ነው፡፡

   የኢራን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሮሀኒ በበኩላቸው፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሁለቱ አገራት ድንበር ላይ ለመገንባት ያቀዱትን የግንብ አጥር በተመለከተም፣ ‹‹አሁን ጊዜው ግንብ የሚገነባበት አይደለም፤ የበርሊን ግንብ ከበርካታ ዓመታት በፊት መፍረሱን እንኳ ዘንግተውታል፤ ወቅቱ  በአገራት መካከል ያለውን ርቀት ለማስፋት ሳይሆን በሰላም አብሮ ለመኖር ደፋ ቀና የሚባልበት ዘመን ነው›› ብለዋል፡፡         

ዓለም በስልጣኔ፣ በቴክኖሎጂ፣ በሳይንስ እና በተለያዩ መንገዶች የተሳሰረችበት ዘመን በመሆኑ እንኳን አዲስ ግንብ ሊገነባ ከዚህ ቀደም በሀገራት መካከል የተገነባ አጥር ካለ እንኳን ሊፈርስ እንደሚገባም ፕሬዚዳንት ሮሀኒ ተናግረዋል፡፡  

የቱርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤናሊ ዪልድሪም፣ “የአሜሪካ ሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ስደተኞች ላይ ያስተላለፉት ውሳኔ ለየትኛውም ችግር መፍትሄ አይሆንም” በማለት ውሳኔውን በጥብቅ ኮንነውታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ ችግሮች የሚፈቱት በሮችን ዝግ በማድረግ እንዳልሆነና እንዲያውም ምዕራባውያን አገራት ቱርክ ያለባትን የሥደተኞች ጫና ሊያግዟት እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ 

  የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ የተቃውሞውን ያህል አይሁን እንጂ ተቀባይነትንም አግኝቷል፡፡ ‹‹ውሳኔያቸው ጥሩም ሆነ መጥፎ ቃላቸውን የጠበቁ ፕሬዚዳንት ናቸው›› የሚሉ አካላትም አልጠፉም፡፡  

የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ተርጓሚ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ቦብ ጉድሌት፣ “ፕሬዚዳንቱ ህገ መንግሥቱ የሰጣቸውን ስልጣን ተጠቅመው የአሜሪካንና የአሜሪካውያንን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ የወሰዱት ትክክለኛ እርምጃ ነው፤ ውሳኔው ማን ወደ አሜሪካ እንደሚገባ በጥንቃቄ ለመመርመርና ለማወቅ ዋስትና ይሰጣል፤ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅትና በሹመት ንግግራቸው ቃል የገቡትን እየፈፀሙ በመሆኑ በፕሬዚዳንቱ ተግባር ደስ የሚሰኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን እንዳሉ መዘንጋት የለብንም” በማለት ለፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ይሁንታ ችረዋል፡፡   

በአውሮፓ ስር እየሰደደ የመጣው የቀኝ ዘመም ፖለቲካ አቀንቃኞች የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ እነርሱም ወደፊት በየአገሮቻቸው ለሚዘረጓቸው ስደተኛ ጠል የሆኑ የአስተዳደር ስርዓቶች ተስፋ ነው ብለው በማሰብ ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡ 

የቼክ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ሚሎስ ዜመን የፕሬዝዳንት ትራምፕን ውሳኔ “አገራቸውን ለመጠበቅ የወሰዱት እርምጃ ነው” በማለት ውሳኔውን አድንቀው፣ የአውሮፓ ኅብረትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

በፀረ-እስልምና አቋማቸው የሚታወቁትና የደች ቀኝ ዘመም ፓርቲ ለነፃነት (Dutch Far-Right Party for Freedom) መስራችና ሊቀመንበር ጌርት ዊይልደርስ፣ “ከስጋት ነፃ መሆን የሚቻልበት ብቸኛው አማራጭ ይህ በመሆኑ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጥሩ አድርገዋል፤ እኔም ብሆን የማደርገው ይህንኑ ነው፤ እንደ ሳዑዲ አረቢያ ያሉ ሌሎች ተጨማሪ እስላማዊ አገራትም በዝርዝሩ ውስጥ እንደሚካተቱ ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት በዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡ 

ብሪታንያ ከአውሮፓ ኅብረት እንድትወጣ የዘመቻው ፊታውራሪ የነበሩት ኒጌል ፋራጅ “ዶናልድ ትራምፕ የተመረጡት’ኮ አገራቸውን ከአሸባሪዎች ለመጠበቅ ነው፤ ውሳኔው የስራቸው አካል ስለሆነ ተገቢ እርምጃ ነው”  ብለው አወድሰውታል፡፡  

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥደተኞች ተቋም (United Nations Refugee Agency) እንዲሁም ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ደግሞ (International Organization for Migration - IOM) በበኩላቸው የትራምፕ አስተዳደር ጦርነትን ሸሽተው ወደ አሜሪካ ለሚጓዙ ስደተኞች ከለላ እንዲሰጣቸው ተማፅነዋል፡፡ መቀመጫቸውን ጀኔቫ ያደረጉት እነዚህ ተቋማት አሜሪካ ስደተኞች ተቀብላ የምታስተናግድበት መንገድ በዓለም ላይ ካሉት ወሳኝ የሥደተኞች ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው እንደሆነ በመግለፅ ፕሬዝዳንቱ ውሳኔያቸውን እንዲያጤኑት ጠይቀዋል፡፡    

የሆነው ሆኖ ገንዘብ እንጂ ፖለቲካ አብሯቸው ያልኖረውና  አገር የመምራት ልምድ የሌላቸው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአወዛጋቢው አቋማቸው ፀሐይ ወጥታ እስከምትጠልቅና ጠልቃ እስከምትወጣ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ማስገረማቸውን፣ ማበሳጨታቸውንና ማስደሰታቸውን ቀጥለውበታል፡፡

 

አብርሃም ተወልደ እና አንተነህ ቸሬ 

Published in ዓለም አቀፍ

ኢሕአዴግን የመታደስ እንቅስቃሴ ውስጥ ካስገቡት መሠረታዊ ጉዳዮች  መካከል የመንግሥት ሥልጣንን የግል ጥቅም ማስከበሪያና የኑሮ መሠረት የማድረግ ዝንባሌ እንደወረርሽኝ መባዛቱ የመጀመሪያውና ዋነኛው ነው። ድርጅታዊ ኃላፊነትን ወደመንግሥታዊ ስልጣን መወጣጫ ዋና መንገድ ተደርጎ መወሰዱም ያፈጠጠው ከዚሁ ከኪራይ ሰብሳቢነት መንሰራፋት ጋር ተያይዞ መሆኑ በየመድረኩ ላይ የተደረጉ ግምገማዎች ሁሉ ያረጋገጡት ጉዳይ ነው። የመንግሥት ሥልጣንን ለበጎ ዓላማ መጠቀም እየቀረ፣ በዝርፊያ ራስን ለመጥቀም ሲውል የድርጅቱንም ሆነ የሚመራውን መንግሥት ህልውና አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መክተቱን ኢሕአዴግ መገምገሙን ተከትሎ በየደረጃው ጥልቀት ያለው ተሃድሶ እየተደረገ መሆኑን መንግሥት አስታውቋል፡፡ በመንግሥት ውስጥም ሆነ ከመንግሥት ውጪ ባሉ ኃይሎች በነጠላም ሆነ በጥምረት ሲፈጸም ለኖረው ቅጥ ያጣ ሙስና መንግሥትና ገዢው ፓርቲ ራሳቸውን የመጀመሪያ ተጠያቂ አድርገው ነው ወደ ተሃድሶው የገቡት። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ በተሳተፉ አመራሮች ላይ መንግሥታቸው እየወሰደ ያለውን ዕርምጃ አጠንክሮ ይቀጥላል ሲሉ በተደጋጋሚ ገልፀዋል። በዚህ እንቅስቃሴ የሙስና ችግር አለባቸው ተብለው ጥቆማ በሚቀርብባቸው አመራሮች ላይ የተጠናከረ ምርመራ እንደሚካሄድ፣ ማስረጃ እስከቀረበ ድረስም መንግሥት ምሕረት እንደሌለውም አረጋግጠዋል፡፡

ህንፃ ያላረፈበት ባዶ መሬት ህንፃ እንዳለው አስመስሎ እንዲሸጥ ማድረግ፣ ከሻጭና ከገዥ ጋር በመመሳጠር በዝቅተኛ ዋጋ እንደተሸጠ አድርጎ ውል ማጽደቅ፣ ፋይሎችን ሆን ብሎ መደበቅ እና ሳይት ፕላን አዘጋጅቶ ለፕላን ማሰሪያ እና መደራደሪያ ማቅረብ፣ የጨረታው መመሪያ በሚያዘው መሰረት ሁሉንም መረጃዎች ሳያካትቱ ወደ ጨረታ ማውጣት፣ ወደ ጨረታ የሚወጣ መሬት ከይገባኛል ነፃ ሳይሆን በችኮላ ማውጣት፣ ከጨረታ በኋላ ከህግና አሰራር ውጭ ተመሳሳይ ስም በማለት ተለዋጭ መሬት መስጠት በዚህም የተነሳ ድሃው እየተጉላላ መሆኑን በጥናቴ አረጋግጫለሁ ያለን መንግሥት እንደገና ማስረጃ የሚፈልገው ከወዴት ነው? በሁሉም ከተሞች እንደተነሳው በመጀመሪያ ለባለሙያውና ለአመራሩ በቤተሰብ፣ በአገር ልጅነትና በጓደኝነት አግባብ ያልሆነ ትስስር ለመፍጠር ይሰራል፣ ያለ ገንዘብ /ጉቦ/ የሚፈፀም ነገር የለም ብሎ የመደምደምና፣ በባለሃብቶቹ በኩል ደግሞ አለማልማትና መሬት አጥሮ ማስቀመጥ እንዲሁም በስታንዳርዶች በትክክል ስለማይሰሩ በጉቦ እንዲፈጸምላቸው ወይም እንዳይጠየቁ ሲሉ ጉቦ የመስጠት ሁኔታ እንደሚታይ እና ይህ ዝንባሌ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ መምጣቱንም በጥናቱ ይፋ ያደረገ መንግሥት በእርግጥም ማስረጃ እየፈለኩ ነው ቢለን የሚያነጋግር እና ተሃድሶውንም አደጋ ላይ እንዳይጥለው የሚያሰጋ ነው፡፡ 

ሌላው የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በመሬት ዙሪያ የሚሰራ አመራርና ሰራተኛ የባለሃብት እና የደላላ ጥገኛ መሆን ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ባለሀብት 70ሺ ብር በማውጣት የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ የአዳማ አመራሩና ሰራተኞች ወደ ትግራይና ደቡብ ክልሎች መላካቸው ባለፈው አመት የፖሊሲ ጥናት ማእከል ባደረገው የጥናት ሰነድ ላይ ተገልጿል፡፡ በዚህም ምክንያት የፈለጉትን ያስወስናሉ፤ ጣልቃ በመግባት ሰራተኛ እንዲባረር ያስደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ የአዳማ ማዘጋጃ ቤት ሰራተኛ ከባለሃብቱ ጋር አለመግባባት በመፈጠሩና እንዲባረር መደረጉም ጭምር፡፡ ስለሆነም በዚህ ተሃድሶ በአዳማ ከተማ ላይ የተደረገው ጥልቅ ተሃድሶ ይህንን ጥያቄም በሚመልስ ደረጃ ካልሆነ ህዝቡ እምነት ያጣል።

ሌላው የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሩ በመሬት ላይ ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት መኖር ነው፡፡ ለምሳሌ በሰበታ አንዳንድ የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም በተለያየ ጊዜ በመሬት ሃላፊዎች ላይ ጫና እንደሚያሳድሩ፤ በከተማው ውስጥ የሚገኙ የቀበሌ አመራሮችና የድርጅት ሃላፊዎች በመሬት ስራ ላይ ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉም በጥናቱ  ተብራርቶ ተገልጿል፡፡ በዚህ ጉዳይ እጃቸው ያለባቸው ከፌዴራል እስከ ከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የኦሮሚያ ባለስልጣናት ላይ ህዝቡ ከዚህ ተሃድሶ አንዳች ነገር እየጠበቀ በሚገኝበት ሰዓት ላይ ማስረጃ ፍለጋው ግራ ቢያጋባን እና መነጋገሪያችን ቢሆን ሊገርም አይገባም።

በተመሳሳይ መልኩ በደቡብ የጥናቱ ግኝቱ እንደሚያሳየው የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባርና አመለካከት በሁሉም ጥናት የተደረገባቸው ከተሞች መስተዋሉ በጥናቱ ተመልክቷል ፡፡ለምሳሌ በዲላ የሃሮ ወላቡ ክፍለ ከተማ ህገ-ወጥ ቤቶች በማፍረስ ሂደት የራስ እና የዘመድ ቤተሰብ ህገወጥ ቤቶች እየመረጡ ሳያፈርሱ ማለፍ እና እንዳይጠየቁ የማድረግ ተግባራት፤ ከዚህም በተጨማሪ በህገ-ወጥ ይዞታ ለያዘው ዘመድ በቶሎ የይዞታ ማረጋገጫ እንዲሰጥ ማድረግ፤ ከዚህ ሌላ አመራሩ ራሱ ህገወጥ ተግባር ላይ እንደሚሳተፍ የተመለከተ ሲሆን፤ ለምሳሌ በሐዋሳ ዳቶ አካባቢ አንዳንድ አመራሮች በህገወጥ ግንባታ በስፋት የተሳተፉበት ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት ይህንን ድርጊት ለማጣራት የገቡ ባለሙያዎች ተሸማቀው ከመመለሳቸውም በላይ ምክንያት ተፈጥሮ በህግ እንዲጠየቁ የተደርጉ መሆናቸውንም በጥናት እንዳረጋገጠ የገለጸ መንግሥት ሃዋሳ ላይ ዛሬም ማስረጃ ፍለጋ ላይ እንደሆነ ሲገልጽ በእርግጥም ግራ ቢያጋባን ሊደንቅ አይገባም፡፡

በሀዋሳና ዲላ ማዘጋጃ ቤቶች ከመዝገብ ቤት ጀምሮ ፋይል የመደበቅና ባለጉዳይ የማጉላላት ችግሮች ያሉ ቢሆንም አመራሩ እያየና እየሰማ እንዳልፈታውና ባለጉዳይን ማጉላላት፣ ማጭበርበር፣ ቶሎ ምላሽ አለመስጠትና ጉቦ መቀበል በዋነኛነት የሚታይ ግልፅ ችግር እንደሆነ፤ የሚወጡ የሊዝ ጨረታዎች አንድ ሰው ከአንድ ጨረታ በላይ ሰነዶችን እንዲገዛቸው ማድረግ እየተለመደ የመጣ ችግር እንደሆነም መታየቱ በጥናቱ ተገልጧል፡፡

ሌላው በዚህ ክልል የታየው የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ ጠባብነት ነው፡፡እንደ ጥናቱ ግኝት በአንዳንድ የደቡብ ክልል ዞኖች ባለሙያን ቀጥሮ ከማሰራት ይልቅ የራስ /የአካባቢ/ ባለሙያ ከሚማርበት ተመርቆ እስኪመጣ መጠበቅ አለ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በህገወጥ ግንባታ በማፍረስም ሂደት የጠባብነቱ አመለካከትና ተግባር እየታየ እንዳለና በዚህ ምክንያት ሁልጊዜ አመራሮች እና ባለሙያዎች ከህዝቡ ጋር የሚጋጩ መሆናቸው ታይቷል፡፡ አመራሩ የጠባብነት አመለካከትና ተግባር ተዋናይ በመሆኑ ለከተማው ዕድገትና ለመሬት ልማት ከፍተኛ እንቅፋት መሆኑን ነው ጥናቱ የሚያሳየው፡፡ ከጠባብነት አመለካከት የተነሳ ቅድሚያ የማግኘት መብት ያላቸውና በቦታው ሲሰሩ የነበሩትን ወደ ጎን በመተው ለሌሎች አሳልፈው መስጠት ሁሉ ስለመኖሩ በጥናቴ አረጋግጫለሁ የሚል መንግሥት ዛሬም ማስረጃ ፍለጋ ላይ ነኝ ማለቱ ውሃ አያነሳም፡፡

በተለይ የከፋ የጠባብነት ችግር የታየው በወልቂጤ ከተማ ነው፡፡ በወልቂጤ ከተማ ከጊዜ ወደጊዜ  ህገወጥ ግንባታ እየተስፋፋ ቢሆንም አመራሩ የቀቤናና የጉራጌ ብሔር የሚለውን የጠባብነት ክፍፍል አስወግዶ እርምጃ እንደማይወስድ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም የጠባብነት ችግር በተለያያ ደረጃ በሃዋሳና በዲላም  እንደሚንጸባረቅ ጥናቱ ያሳያል፡፡ ያም ሆኖ ግን በዚህ ጥልቅ ተሃድሶ መንግሥት በወልቂጤ ሃዋሳና ዲላ በስንቶቹ አመራሮች ላይ እርምጃ መውሰዱን አለመግለጹ ሳያንስ ማስረጃ እያፈላለኩኝ ነው ቢል የህዝቡን ጥያቄ መመለስን እና የተጀመረውን ልማት ማስቀጠልን አላማ ያደረገው ጥልቅ ተሃድሶ ውሃ እንዲበላው መፍቀድ ይሆናል።

 በመቀሌ ደግሞ ሁለት ዓመት የተፈረደበት እስረኛ ወጥቶ መኪናውን ይዞ ሲንጎማለል ሰው በመግጨት እንደገና መያዙን በማረጋገጥ የኪራይ ሰብሳቢነት አጀንዳ ውስጥ የተዘፈቁ አመራሮች ስለመኖራቸው በጥናቱ ያረጋገጠ መንግሥት ማስረጃ በማጣቱ ዛሬም የክልሉ አመራሮች በሞቀው ወንበራቸው ላይ መገኘታቸው ተሀድሶው ተረት ሆኖብናል።

በአዲስ አበባ የተደረገው ጥናት እንደሚያ መለክተውም አመራሩ የቁርጠኝነት ችግር እንዳለበትና በኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የተዘፈቀ እንደሆነ፤ የመሬት ወረራና ሕገ-ወጥ ግንባታን እንዳላወቀ ማለፍ፤ በጥቅም ትስስር ምክንያት በህዝቡ የሚነሱ እሮሮዎችን ቸል ማለት፤ ሕዝብን ማስለቀስ፤ ማመናጨቅ፤ ማሸማቀቅ፤ ከሰራተኞች ጋር ተግባብቶ አለመስራት፤ አድሎአዊነት (የአንዱን የህገ-ወጥ ግንባታ አፍርሶ የሌላውን መተው) በሰፊው እንደሚስተዋል በጥናት ሰነዱ ተመልክቶ ሳለ የከተማው አስተዳደር የካቢኔ አባላት ላይ እንኳንስ እርምጃ ሊወሰድ ከወንበራቸውም ፍንክች ሳይሉ ማስረጃ እየተፈለገባቸው ነው ስንባል አንገት ያስደፋናል። 

ባለጉዳይን “በእጅህ ካልመጣህ አገልገሎት አታገኝም” ብለው ቁርጡን የሚናገሩም እንዳሉ በጥናቱ ተጠቀሷል፡፡ በተለይ በስም ዝውውር ላይ በፈጻሚዎች ደረጃ፤ መሃንዲሶች ደግሞ የወሰን ችካል ሲሰሩ፣ ኢንቬንቶሪ ሲወስዱ፣ የግንባታ ፈቃድ ሲሰጡና የስም ዝውውር ሲሰሩ ትልቅ የኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት ይፈጸማል፤ በተጨማሪም መሃንዲሶች የራሳቸውን የግል ስራ በመንግሥት ስራ ሰዓት እና በመንግሥት ማቴሪያል በመጠቀም እንደሚሰሩና በተለይ የፕላን ስምምነት ሥራን በተመለከተ ትልቅ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭ ስለሆነ ባለጉዳይ ይዞ የሚመጣውን ፕላን መሃንዲሶቹ ከሚያቋውቸው ሰዎች ውጪ ተሰርቶ ከመጣ ሰበብና እንከን በማፈላለግ እንደማያጸድቁላቸው/ እንደሚያንገላቷቸው አመራሩም እያወቀ እርምጃ እንደማይወሰድ ወዘተርፈ በጥናቴ አረጋግጫለሁ የሚል መንግሥት ዛሬም በሃገር ደረጃ ማስረጃ ያገኘሁባቸው ከ120 ያልዘለሉ ናቸው ሲለን እየተደረገ ያለው ጥልቅ ተሃድሶ ሳይሆን የሌላ ያስመስልበታልና መንግሥታችን በቶሎ ወደቀልቡ እንዲመለስ እንሻለን፡፡

 በአጠቃላይ፣ ሙስናም ይባል ኪራይ ሰብሳቢነት ወይም ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት ከሥርዓቱ በተጨማሪ የአገርም አደጋ ነው፡፡ ጥልቅ ተሃድሶው የሃገርን ህልውና በዘላቂነት ታሳቢ ካላደረገ አደጋ አለው፡፡ በመፈራራት ወይም በእከከኝ ልከክህ እሳቤ ለመቀጠል ማሰብም ሆነ፣ የሕዝቡን ጥያቄ ከተገቢው ጊዜ በላይ በማራዘም መልስ መንፈግ ውጤቱ ጥሩ አይሆንም፡፡ ከላይ በተመለከተው አግባብ በመልካም አስተዳደር ችግሮችና በሙስና ላይ ጥናት አካሂዶ አስገራሚ መረጃዎችን ማቅረብ የቻለውን የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ማዕከል ኢንስቲትዩት ይዞ፣ ማስረጃ ፍለጋ ሌላ ቦታ መባዘን ለአገር  አይጠቅምም፡፡ ለሃገርና ለሕዝብ ዘለቄታዊ ሰላምና መረጋጋት ሲባል ሕግ እንዲከበር አስፈላጊው ሁሉ መደረግ አለበት የዚህ ፅሁፍ የማጠቃለያ መልእክት ነው፡፡ 

 

ስሜነህ

Published in አጀንዳ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።