Items filtered by date: Monday, 06 February 2017

 

በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅና ተናፋቂ የሆነው የአፍሪካ ዋንጫ፤ 60ኛ ዓመቱን በጋቦን አክብሯል። በግብጽ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ ጠንሳሽነት የተጀመረው ውድድሩ፤ እ..አ ከ1957 ጀምሮ በየሁለት ዓመቱ እየተካሄደ 31ኛው ላይ ደርሷል። የ2017ቱ የአፍሪካ ዋንጫም በ16 ብሄራዊ ቡድኖች መካከል ብርቱ ፉክክር ሲደረግበት ሰንብቶ ትናንት ተጠናቋል። በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የታዩና የተከሰቱ ልዩና አስደናቂ ጉዳዮችንም እናስቃኛለን ተከተሉን፡-

                                          ***

በአውሮፓ ሊጎች ከሚሳተፉ ተጫዋቾች መካከል አብዛኛዎቹ ከሌሎች አገራት የሚፈርሙ ናቸው። በዚህ ምክንያትም የአፍሪካ ዋንጫ፣ የኮፓአሜሪካ ዋንጫና ሌሎች አህጉር አቀፍ ውድድሮች ሲካሄዱ በሊጎቹ መቀዛቀዝ ይፈጠራል። በዚህ የአፍሪካ ዋንጫም በአውሮፓ ተወዳጅ ከሆኑት ሊጎች ቀዳሚ ከሆነው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ብቻ፤ የትውልድ አገራቸውን ለመወከል 24አፍሪካውያን ተጫዋቾች ጋቦን ተገኝተዋል።

                                           ***

በአፍሪካ ዋንጫው እየተሳተፉ ካሉ ተጫዋቾች መካከል ግብጻዊው ኢሳም ኤል ሃድሪ አንጋፋው ተጫዋች ነው። የ43 ዓመቱ ጎልማሳ በግብ ጠባቂነት አገሩን በመወከል በርካታ ጨዋታዎች ላይ የተሳተፈ ሲሆን፤ ከጋቦኑ የአፍሪካ ዋንጫ በፊት 4ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል። በተቃራኒው የ18 ዓመቱ ሴኔጋላዊ ኢስማኤል ሳር ወጣቱ ተጫዋች በሚል ተመዝግቧል።

                                         ***

ኡጋንዳ ከ39ዓመታት በኋላ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊነቷን ያረጋገጠች አገር ናት። ክስተቱን ለየት የሚያደርገው ደግሞ እ..አ በ1978 ኡጋንዳን ከውድድር ውጪ ካደረገቻት ጋና ጋር በምድብ «D» መደልደሏ ነው። ኡጋንዳ ወደ ዋንጫ ሽሚያው ከዓመታት በኋላ ስትገባም ከጋና ጋር የተጫወተች ሲሆን፤ ታሪክ ራሱን ደግሞ የ10ተሸናፊ አድርጓታል።

                                         ***

16አፍሪካውያን አገራትን ያሳተፈው የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በአፍሪካውያን አሰልጣኞች የሚመሩ አገራት እጅግ አንሰው የተገኙበት ነበር። በአፍሪካውያን አሰልጣኞች ፊት አውራሪነት የቀረቡት ቡድኖት አራት ብቻ ሲሆኑ፤ እነርሱም ዚምባብዌ፣ ሴኔጋል፣ እንግዳዋ አገር ጊኒ ቢሳዎ እንዲሁም ዴሞክራቲክ ኮንጎ ናቸው።

                                         ***

ከረጅም ዓመታት በኋላ የአፍሪካ ዋንጫን የተቀላቀለችው ኡጋንዳ አንድም የኡጋንዳ ተወላጅ የሆነ ተጫዋች ያላሰለፈች አገር ተብላለች። ቱኒዚያ በተቃራኒው በርካታ ትውልደ ቱኒዚያውያን ተጫዋቾችን ያሳተፈች አገር ሆናለች።

                                      ***

የግብጹ ታዋቂ ክለብ አል-ሃሊ በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ በርካታ ተጫዋቾችን ለብሄራዊ ቡድኖች ያስመረጠ ክለብ ሆኗል። ክለቡ 7ተጫዋቾችን በማስመረጡም ነው ቀዳሚ የሆነው።

 

ብርሃን ፈይሳ

 

Published in ስፖርት

ጉዳት ከማያስተናግዱ ሰላማዊ ጨዋታዎች መካከል አንዱ ነው። መቼ እንደተፈጠረ የማይታወቀው ይህ ጨዋታ ምናልባትም በጥንታዊቷ ግብጽ ይዘወተር ይሆናል የሚል መላምት በባለሙያዎች ይቀርባል። ለዚህ መላምት መነሻ የሚሆነውም በጥንታዊቷ ግብጽ ኳስን በመጠቀም የሚካሄዱ በርካታ ጨዋታዎች መኖራቸውን በቁፋሮ የተገኙ ቅርጻ ቅርጾችና ስዕሎች የሚያሳዩ በመሆኑ ነው። የሥነ ምድር ተመራማሪዎችም ከእነዚህ ጨዋታዎች መካከል አንዱ ቢሊያርድ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አላቸው።

ቢሊያርድ ተወዳጅነቱና ተዘውታሪነቱ ጎልቶ የታየው በ15ኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን፤ በሰሜን አውሮፓ አገራት በተለይም በፈረንሳውያን ዘንድ የተለመደ መሆኑን የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ። ቢሊያርድ የሚለው ስያሜ የተገኘው ከሁለት ቃላት ጥምረት ሲሆን፤ «ቢላርት» የእንጨት ዱላ «ቢሊ» ደግሞ ኳስ ከሚለው የፈረንሳይ ቋንቋ የተወረሰ ነው። በወቅቱም በንጉሳውያን ቤተሰቦች እንዲሁም የተከበረ ሥራ ላይ ባሉ ሰዎች ይዘወተርም ነበር።

ጨዋታው በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ ዘመን የተስፋፋና ያደገ ሲሆን፤ ቀድሞ በዝሆን ቀንድ በተሰራ ኳስ ይካሄድ የነበረው ጨዋታ በፕላስቲክ ተተክቷል። አሁን ያሉት ሦስት የቢሊያርድ ጨዋታዎች (ግራውንድ ፑል፣ ፑልና ከረምቡላ) በዚሁ ጊዜ ህግና ደንብ ወጥቶላቸው መካሄድ መጀመራቸውን ታሪክ ያስረዳል። ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተጀምረውም አገራት ከአገራት ጋር መፎካከር ችለዋል።

ይህ ጨዋታ በኢትዮጵያም በመስፋፋትና በመዘውተር ላይ ያለ መሆኑ ይታወቃል። በተለያዩ ሆቴሎች የመዝናኛ ቦታዎችና በየአካባቢው በተለይ የፑልና ከረንቦላ ጨዋታዎች ከልጅ እስከ አዋቂ ያለው ህብረተሰብ ተሳታፊ ይሆንባቸዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ አካላት ጨዋታውን ከማዘውተርና ጊዜያቸውን በጨዋታው ከማሳለፍ ባሻገር ህግና ደንቡን በትክክል እየተገበሩት አይደለም። በትክክለኛው መንገድ ቢሰራበት ግን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልትወከልበት የምትችለው የጨዋታ አይነት ይሆናል።

ይህንን በማሰብም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጨዋታው አገር አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ የማድረጉ ሥራ ኮሚቴ በማቋቋም እየተከናወነ ነው። ኮሚቴው ከተቋቋመ ዘጠኝ ዓመታትን ያስቆጥር እንጂ በሚፈለገው መልኩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች አለመከናወናቸውን የኮሚቴው ፕሬዚዳንት አቶ ይርጋ አበጋዝ ይገልጻሉ። በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ጥቂት ክለቦች ቢኖሩም፤ ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር በማጣጣም የራሱ ሕግና ደንብ ወጥቶለት ውድድር እየተካሄደበት አይደለም። በመሆኑም የክለቦቹ ቁጥር እየተመናመነ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ያስረዳሉ። የክለቦቹን ቁጥር ለማስፋት እንዲሁም ጨዋታው በህብረተሰቡ ዘንድ ዕውቅና አግኝቶ ወደ ፌዴሬሽን እንዲያድግ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ በሌሎች ክልሎች መስራት እንደሚገባም ይጠቁማሉ።

የቢሊያርድ ጨዋታ ዕድሜና ጾታን የማይለይ ሲሆን፤ አካል ጉዳተኞችንም ያካትታል። አእምሮን ከማዝናናት ባለፈም የማቀድና ዕቅድንም ወደ ተግባር የመለወጥ ችሎታን ያሳድጋል። ቢሊያርድን መጫወት ማህበራዊ ግንኙነትን የሚያጠናክር ሲሆን፤ በጨዋታው ወቅት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችም ነጻ ጅምናስቲክ የተባለውን እንቅስቃሴ ለማጎልበት ይረዳሉ።

 

ብርሃን ፈይሳ

Published in ስፖርት

«የቤኒሻንጉል አፈር ቢቆፈር ውሃ ሳይሆን ወርቅ ያፈልቃል» ይባላል። ምድሩ ወርቅ ብቻም ሳይሆን ወርቃማ ስፖርተኞችንም ያፈራ ነው። ባሳለፍነው ዓመት በተካሄደው የሪዮ ኦሊምፒክ ከወርቅ በላይ ደምቃ የታየችው አትሌት አልማዝ አያና የዚሁ ክልል ፍሬ ናት። የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን ከሚወክሉት ቁልፍ የእግር ኳስ ተጫዋቾች መካከልም ሰለሃዲን ሰኢድ ሌላኛው የክልሉ ሃብት ነው። እነዚህን ብርቅዬ ስፖርተኞች ያፈራው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዚህ ወቅትም ተተኪ ወጣቶችን በማፍራት ሥራ ላይ ተጠምዷል።

ክልሉ ካለው የህዝብ ብዛት ውስጥ 30 ከመቶ የሚሆኑት ወጣቶች ናቸው። እነዚህን ወጣቶች ደግሞ በተለያዩ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ ለክልሉም ሆነ ለአገሪቱ የሚኖረው ፋይዳ የላቀ ነው። በዛሬው እትማችንም በክልሉ ስላለው አጠቃላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ፣ የማዘውተሪያ ስፍራዎች የማስፋፋት ሁኔታ፣ የሴቶችና ወጣቶች ስፖርታዊ ተጠቃሚነት፣ የክልሉ ዋነኛ የስፖርት ዘርፍ ችግሮች እንዲሁም መልካም አጋጣሚዎችና ፈተናዎችን አስመልክቶ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ያደረጉትን ቆይታ እነሆ!

አዲስ ዘመን፡- ክልላችሁ በቅርቡ ለሁለት ስፖርተኞች እውቅና መስጠቱ የሚታወስ ነው፤ የዚህ መነሻ ምክንያቱ ምን ነበር?

አቶ ደስታየሁ፡- በስፖርቱ መስክ ክልሉን ያስጠሩ ሰዎችን የማበረታታት ሥራ ጀምረናል፤ ይህ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል። በዚህ ዓመት የአገራችንን ስም ካስጠሩት ስፖርተኞች መካከል አትሌት አልማዝ አያና በእግር ኳስ ደግሞ ለሰላዲን ሰይድ እውቅና ሰጥተናል። ይህም ተተኪዎችን በብቃት እና በሥነ ልቦና ጠንካራ ሆነው ለቀጣይ ሥራ እንዲዘጋጁ ያደርጋቸዋል። በአጭሩ በስፖርቱ ውጤታማ የሆኑትን በመሸለም ሌሎች ውጤታማ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚለው የእውቅናው ዋነኛ መነሻ ሃሳብ ነበር።

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ በየትኛው የስፖርት ዘርፍ ነው የተለየ አቅም አለኝ ብሎ የሚያምነው ?

አቶ ደስታየሁ፡- በክልሉ የተለየ አቅም ያለበትን ቦታ ለይተናል። በተለይ እግር ኳስ አዋጭ እንደሆነ በመገንዘባችን፤ ፕሮጀክቶችን ቀርፀን ድጋፍ በማድረግ ላይ እንገኛለን። በቀጣይ ሰለሃዲንን የመሳሰሉ በርካታ ወጣቶችን የማፍራት ውጥን አለን። በአትሌቲክሱም ቢሆን ወደ መተከል ዞን ተተኪዎችን ለማፍራት አመቺ ሁኔታዎች እንዳሉ ተገንዝበናል። ይህን አጠናክሮ እና ክትትል አድርጎ ተተኪዎችን ማፍራት የግድ የሚለን በመሆኑ የተቻለንን ሁሉ እያደረግን ነው። በቅርብ ዓመታት ውስጥ አገሪቱን የሚያስጠሩ በርካታ ስፖርተኞችንም ማፍራት እንችላለን። ለዚህም ሌት ከቀን እየሰራን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ክልሎች ተተኪዎችን ከማፍራት አኳያ ውስንነት እንዳለባቸው ይነገራል። ከዚህ አኳያ በክልሉ ምን እየተከናወነ ነው?

አቶ ደስታየሁ፡- ተተኪዎችን ለማፍራት ክልላችን የመካከለኛ እና ረጅም ጊዜ እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው። በተለይ ስፖርት ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ለማስፋፋት፣ ተተኪዎችን በብዛት እና በጥራት ለማፍራት እንዲሁም ሁሉንም የስፖርት ዓይነቶች የማስፋፋት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። በክልሉ ባሉ 20 ወረዳዎች ውስጥም 91 የወጣት ፕሮጀክቶች ተከፍተው፤ በ13 የስፖርት ዓይነቶች ከ2300 በላይ ወጣቶች ስልጠናቸውን እየተከታተሉ ነው። እነዚህ ፕሮጀክቶችም ከ1315 እና 17 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊ ወጣቶችን ያካተቱ ናቸው።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካለው የህዝብ ብዛት ውስጥ 30 ከመቶ የሚሆኑት ወጣቶች ናቸው። እነዚህን ወጣቶችም በተለያዩ ተግባራት እንዲሳተፉ ማድረግ ለክልሉም ሆነ ለአገሪቱ የሚኖረው ፋይዳ የላቀ ነው። በዚህ ሂደትና ጥረት ውስጥም ተጨባጭ ለውጦችን እየተመለከትን ስለሆነ በፕሮጀክቶች ላይ ማተኮር እንዳለብን ተገንዝበናል። ይህም የፍላጎት ጉዳይ ሳይሆን ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለመጣጣም ታዳጊዎች ላይ ማተኮር ግድ ይለናል። በአሁኑ ወቅት የጀመርነው ተተኪዎችን የማፍራት ጥረት በጥቂት ዓመታት ውስጥ በክልል፣ በአገርና በአህጉር አቀፍ ደረጃ ውጤታማ ወጣቶችን ለማፍራት ያግዘናል የሚል እምነት አለን።

አዲስ ዘመን፡- በዚህ የስፖርት ማዕቀፍ ውስጥ ክልሉ ምን ያክል ሴቶችን እያሳተፈ ነው?

አቶ ደስታየሁ፡- ሴቶችን በስፖርት ተጠቃሚና ተሳታፊ ለማድረግ አቅደን እየሰራን ነው። ከትምህርት ቤት እና ታዳጊዎች ጀምሮ በፕሮጀክቶች በመታቀፍ በ13 የስፖርት ዓይነቶች እየሰለጠኑ ነው። ሴት አሰልጣኝ እና ዳኞችን የማፍራት ጉዳይም ዋነኛው አጀንዳችን ነው። በዚህ ረገድ ባሳለፍነው ዓመት ውጤታማ ሥራዎችን ሰርተናል። በአሁኑ ወቅትም የአሰልጣኞች አሰልጣኝ የሆኑ ሴቶችን በሁሉም የስፖርት መስክ እያፈራን ነው።

አዲስ ዘመን፡- በየወረዳው ያሉት የወጣት ፕሮጀክቶች በስፖርቱ የክህሎት ስልጠና ከመውሰድ ባለፈ ስፖርታዊ ጨዋነት ተላብሰው እንዲያድጉ ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ደስታየሁ፡- ስፖርት እና ስፖርታዊ ጨዋነትን ለያይተን ማየት አንችልም። ፕሮጀክቶቹ ሲቀረጹ ይህንን ማካተት አለባቸው የሚል ጽኑ እምነት አለን። አንድ ስፖርተኛ ስፖርታዊ ጨዋነትን ካላሳየ ምሉዕ ነው ማለት ያስቸግራል። በመሆኑም ሰልጣኞቹ በተቻለ መጠን ስፖርታዊ ጨዋነትን ጠንቅቀው እንዲገነዘቡና እንዲተገብሩም ጭምር ነው ታሳቢ የተደረገው። ይህንንም በተለያዩ ውድድሮች ላይ እየታዘብን ነው። አፈንግጠው የሚወጡ ችግሮች ካሉም በሂደት እንዲስተካከሉ ይደረጋል። ስፖርት እና ስፖርታዊ ጨዋነት ተናበው መሄድ ስላለባቸው አበክረን እየሰራን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ተተኪዎችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማመቻቸትና ማስፋፋት ቀዳሚው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ክልሉ ምን እየሠራ ነው?

አቶ ደስታየሁ፡- የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በገጠርም ሆነ በከተማ በማስፋፋት ላይ እንገኛለን። ለአብነት ያህልም 30ሺ ተመልካቾችን የሚይዝና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በአሶሳ ከተማ እየተገነባ ነው። የዚህ ስታዲየም ግንባታ በአሁኑ ወቅት ሁለተኛው ምዕራፍ ተጠናቆ ለሦስተኛው ምዕራፍ የግንባታ ሂደት ከተቋራጩ ጋር ልንፈራረም ነው። ከዚህ ባለፈም በሁሉም ቀበሌዎች የስፖርት ማዘውተሪ ስፍራዎችን የማስፋፋቱ ሥራ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ሆኗል። ይሁንና እነዚህ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች የጥራትና ደረጃቸውን ያለመጠበቅ ችግሮች አሉባቸው። ለሁሉም ማዘውተሪያዎች የይዞታ ማረጋገጫ አለመኖርም ትልቅ ፈተና ነው። ይህንን ችግር ለማቃለልም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በተደጋጋሚ ውይይት ሲደረግ ቆይቷል። መግባባት ላይ እየተደረሰ ስለሆነም በሂደት መፍትሄ ይገኛል ተብሎ ይታሰባል።

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ያሉት ፕሮጀክቶች የሚጠቀሙባቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እውቅና አላቸው?

አቶ ደስታየሁ፡- የስፖርት ማዘውሪያ ስፍራዎች ሊከለሉ፣ እውቅና ሊያገኙና የይዞታ ማረጋገጫ እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል። በየጊዜውም እንደ አስፈላጊነቱ ሊጸዳና ሊጠረግም ይገባዋል። ነገር ግን አብዛኞቹ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎቻችን እውቅና የላቸውም። የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳታችንም በከተማ የሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እውቅና እንዲያገኙ ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ እንዲሁም ከከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ጋር ሆነን እየሰራን ነው። በገጠር አካባቢ የሚገኙት የስፖርት ማዘውተሪያዎች ደግሞ ከገጠር መሬት አስተዳደር ቢሮ ጋር በመቀናጀት የይዞታ ማረጋገጫ እንዲሰጣቸውና እንዲረጋገጥላቸው በጋራ እየሠራን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች አንዱ የሆነው የአሶሳ ስታዲየም ግንባታ ዘግይቷል የሚል ቅሬታ ይቀርባል። ቢሮው ለዚህ የሚሰጠው ምላሽ ምንድነው?

አቶ ደስታየሁ፡- የስታዲየሙ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እየተካሄደ ነው። ሆኖም ከግንባታ ዲዛይን መሻሻል ጋር በተያያዘ ትንሽ ዘግይቷል። ሁለተኛው የግንባታ ምዕራፍ መቶ በመቶ ተጠናቋል። ለሦስተኛው ምዕራፍም የሰነድ ዝግጅት ተጠናቆ ከተፈራረምን በኋላ ወደ ሥራ ይገባል። የክልሉ ህዝብ በሚያደርገው እገዛ እና መንግሥት በሚመድበው በጀትም ክትትል እያደረገ ነው። በተያዘለት መርሐ ግብር ይጠናቀቃል የሚል እምነት አለኝ፤ ስለዚህም ይህን ያህል አሳሳቢ ጉዳይ አይደለም።

አዲስ ዘመን፡- ስፖርቱን ለማሳደግ የራስን ገቢ የማንጨት እና ክልሉም በብሄራዊ ደረጃ የሚወከልበትን ክለብ ለማፍራት የተጀመረ ጥረት ይኖር ይሆን?

አቶ ደስታየሁ፡- ስፖርቱን ከመንግሥት ድጎማ በማላቀቅ በራሱ አቅም እንዲንቀሳቀስ በማድረግ አኳያ የስፖርት ሃብት አሰባሰብ ሥርዓት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው። በክልሉ የተሻለ የስፖርት ገቢ ሥርዓት ለስፖርቱ ዕድገት በሚፈይድ መልኩ እየተሰራበት ነው። ይህም የላቀ ለውጥ እንደሚያመጣ እንጠብቃለን።

ክልሉ የአገራችንን ስም ያስጠሩ እንደ ሰላሃዲን ሰኢድ ዓይነት የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ያፈራ ነው። ይህንን ለማስቀጠልም ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ቤጉ ሊግ (ቤኒሻንጉል ሊግ) እንዲካሄድ ተደርጓል። በዚህ ዓመት ደግሞ 10 ክለቦች በቤጉ ሊግ ለመሳተፍ ጥያቄ አቅርበዋል። ይህም በቀጣይ የሚወሰን ይሆናል። በብሄራዊ ሊግ ደረጃም ለመጀመሪያ ጊዜ የአሶሳ ከነማ ክለብ አቋቁመን እየተሳተፍን ነው። ይህ በክልሉ ስፖርት ዕድገት ላይ የሚኖረው አንድምታም እጅግ የላቀ ነው።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ክልል የስፖርቱ ዋነኛ ችግሮች ምንድን ናቸው?

አቶ ደስታየሁ፡- ጥራት ዋነኛው ችግር ነው። ታዳጊ ፕሮጀክቶች ላይ ያለው የስልጠና አሰጣጥ ጉዳይም ሌላው ፈተናችን ነው። በተለይ ብቃት ያለው አሰልጣኝ፣ ጥቅማ ጥቅም እንዲሁም ከዓለም ነባራዊው ሁኔታ ጋር በመረጃዎች እና በቴክኒክ የተደገፈ ስልጠና መስጠቱ ሌላው ጉዳይ ነው። እነዚህ ደግሞ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በስፖርቱ ላይ ያላቸው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም።

 

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

 

Published in ስፖርት
Monday, 06 February 2017 19:04

ሳልና ስርቆት

 

ኡሁ!…ኡሁ!…

ረሃብ የጠናበት

አባባል መች ያውቃል

ይሉኝታውን ትቶ

ሳል ይዞ ይሰርቃል

...

ኡሁ!…ኡሁ!…

እኔም ይሉኝታ ቢስ

ሳል ይዤ እሰርቃለሁ

ቅቤ ልቤን ይዤ

ፀሐይ እሞቃለሁ

 

ልዑል ኃይሌ

 

Published in መዝናኛ

በምንኖርበት ምድር ሁሉም ነገሮች ሊገለፁ የሚችሉ አይደሉም። አንዳንዶቹ እንዲያውም ለመግለፅ ባላቸው አዳጋችነት ልክ ሳቢና ማራኪ ሆነው እናገኛቸዋለን። እንዲህም ዓይነት ተፈጥሮ አለ እንዴ? በሚል በግርምት እንድንጠይቅ የሚያደርጉ ነገሮች ያጋጥማሉ። ለዛሬም ሊስት ቨርስ የተሰኘው ድረ-ገፅ በዓለማችን ላይ ምስጢራዊ ቦታዎች ናቸው ብሎ ካሰፈራቸው መሀል የቻይናውያኑን የአጭር ሰዎች መገኛ እናያለን።

አካባቢዎች በባህሪያቸው አዲስ ነገር አይደሉም። እንግዳም አይደሉም በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች ሰዎች ተሰባስበው አካባቢን ይፈጥራሉ። በዓለማችን በሕዝብ ብዛቷ የምናውቃት ቻይና ከሕዝብ ቁጥር ባሻገር አስገራሚ የሰዎች ስብስብ ያለበት አካባቢም አላት። ሲቿን ግዛት የሚኖሩት የያንግሲ ማህበረሰብ አባላት የተለያዩ ሳይንቲስቶችን አትኩሮትና ቀልብ መግዛት የሚችል ነገር አላቸው። ምክንያቱም 80 ነዋሪዎች ከመሆናቸው ባለፈ ድንክዬዎች ወይም በእንግሊዝኛው አጠራር (dwarf) ናቸው።

በአፈታሪክ እንደሚነገረው ከ60 ዓመታት በፊት አካባቢው ባልታወቀ ሁኔታ ህመም ተከስቶ ነበር። በዚህም ምክንያት ዕድሜያቸው ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት ዕድሜ የሚሆኑትን ነዋሪዎች በሽታው በጣም ጎድቷቸውም ነበር። በመሆኑም በሽታው የሰዎቹን የእድገት ሂደት በመግታቱ ሁሉም ታማሚዎች ቁመታቸው ማደግ አልቻለም። ተመራማሪዎች እንደሚሉት እንዲህ ዓይነት ክስተት ሊፈጠር የሚችለው ከ20 ሺህ ሰዎች በአንዱ ላይ ብቻ ነው። ታዲያ የያንግሲ አካባቢ ላይ ምን ተፈጥሮ ነው? እስካሁን መልስ አልተገኘም። በአካባቢው ላይ የተፈጠረው ነገር ከተለመደው ወጣ ያለ እንደሆነም ይነገራል። በተለይ ብዙኃኑ ድንክዬዎች ነዋሪነታቸውን ያደረጉት በሲችዋን ግዛት መሆኑ አስገራሚ ነው።

ያልታወቀው በሽታ ያደረሰው ችግር የከፋ ባይሆንም በአንዳንዶች ላይ ግን ለተለያየ አካል ጉዳትም ዳርጓቸዋል። የዚህ ችግር ተጠቂ የሆኑትም የሚወልዱት ልጅ ከአንድ ሜትር ወይንም ከሦስት ጫማ ቁመት በላይ አያድጉም። የቻይና መንግሥትም ምንም ዓይነት ጎብኚ ወደ አካባቢው እንዲገባ እንደማይፈቅድ ይነገራል። ነዋሪዎቹም የነበረውን ነገርም ለመናገር ከሞከሩ የሚመጣብን ችግር አለ ብለው ስለሚያስቡ አይሞክሩትም። ነዋሪዎቹ በወቅቱ በጥቁር መንፈስ በመያዛቸው እና በዚህም ምክንያት በአያቶቻቸው ጊዜ እንደተረገሙ ያስባሉ። ተገቢ ያልሆነም ቀብር ይፈፅሙ ስለነበር ቁጣ እንደደረሰባቸው አድርገው ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ ኤሊ የችግሩ ምንጭ እንደሆነ ያምናሉ። የአካባቢው ነዋሪ በድሮ ጊዜ ጥቁሩን የኤሊ ዝርያ በማብሰል ይመገቡ እንደነበር ጠቅሰው በዚህ ምክንያት ያንግሲ ባልታወቀ ህመም እንደተመታች ይናገራሉ። ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላም ግን ነዋሪዎቹ ከበሽታው ጋር እየኖሩ እንዳሉ ያመላክታል። አዲሱም ትውልድ የተከተለው ይመስላል። አጫጭሮቹ ትውልዶች ዛሬም ይህችን ዓለም እየተቀላቀሉ ይገኛል።

 

ፍዮሪ ተወልደ

Published in መዝናኛ
Monday, 06 February 2017 19:02

«ሽወዳ»

 

ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ

ሀገርም እንደሰው «ይሸወዳል» ወይ?

የዚህ ዘፈን ግጥም እንዲህ አልነበረም፤ ለዚህ ርዕስ ስል ግን በፈቃዴ ቀይሬዋለሁ። አብዛኛው ጉዳይ ወደ ከተማና ሀገር ከማደጉ በፊት መጀመር ያለበት ከየቤታችን ነው። ስለሆነም ጨዋታዬን ከሁላችን ቤት ልጀምር። ዓውደ ዓመት ሲደርስ አሊያም ሌላ ጉዳይ ኖሮብን ወዳጅ ዘመዶቻችንን ወደ ወደቤታችን ስንጋብዝ ልማድ ሆኖብን ተመሳሳይ ነገር እናደርጋለን። ይኸውም ወትሮ ቸል ያልናቸውን የቤታችንን ጓዳ ጎርጓዳ ማጸዳዳት፣ በየስርቻው የወዳደቁ ዕቃዎችን ሰብስቦ ማጣጠብ፣ ዕቃችንን በፈርጅ በፈርጁ እየደረደርን ለማሰማመርና ለማስዋብ ሽርጉድ እንላለን። በጎደሉት ደግሞ በደህና ጊዜ ያስቀመጥነውን በማውጣትና ከጎረቤትም በመዋስ እንሞላዋለን። ይህ የእኛነታችን መገለጫ ልማድ ሆኗል!!!

ታዲያ ዓውደ ዓመቱ ወይም ዝግጅቱ ተጠናቆ እንግዶቻችንን ወደየመጡበት ስንሸኝ ሁሉንም ወደ ቀደመው ይዞታቸው እንመልሳቸዋለን። ይህ መሆኑ አንድም ክብራችን ለራሳችን ሳይሆን ለሌሎች መሆኑን ያሳየናል። አልያም በምክንያት የወጣው የሚሳሳለት ዕቃ ወደቦታው ሳይመልስ ለጉዳትና ለብልሽት ይዳረጋል። ከዚህ ይልቅ ግን ለራሳችን ክብር ሰጥተን ተገቢውን መንገድ ብንከተል አትራፊ፤ መጨረሻ ላይ ከሚያጋጥመን ወከባ ተራፊ እንሆናለን። «ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ እና የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ» ይሏቸው ተረቶችስ ይህንኑ ምክንያት አድርገው አይደል የተተረቱብን።

ከቤታችን ወጥተን ሀገራችንን ብንመለከትም፤ ይሄ ልማድ ሀገር አቀፍ እንደሆነብን እንረዳለን። ስብሰባ ወይም መሰል መርሃ ግብር ይካሄዳል ሲባል ያረጁትን ማደስ፣ ያልተጀመሩ ግንባታዎችን መቼ እንደተጀመሩ እንኳን ሳይታወቅ ለማጠናቀቅ መጣደፍ፣ ደብዘዝ ያሉትን ማደማመቅ፣ የቆሸሹትን ማጸዳዳት ይከተላል። አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን አንድን ቦታ ይጎበኛሉ ከተባለማ የማይከናወንና የማይገዛ ነገር አይኖርም፤ ባስ ካለም ጎረቤት ከጎረቤቱ ዕቃ እንደሚዋዋሰው የውሰትና የኪራይ ዕቃዎችን የራስ አስመስሎ ማቅረብ ያለ ነው።

በዚህ ልማድ እጅጉን የተሸበበችው መዲናችን አዲስ አበባም፤ ከሰሞኑ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤን ለማስተናገድ ደፋ ቀና ስትል ነው የሰነበተችው። በተለይ መንገዶቿ፤ ቀድሞ ያልነበራቸውን ክብር ማግኘታቸውን መታዘብ ይቻላል። ከዚህ ቀደም እግረኛና ተሽከርካሪን የማይለዩት ጎዳናዎች ሥርዓታቸውን የጠበቁ የመንገድ መለያዎች ተበጅተውላቸው፣ በፊት እስከመኖራቸውም የማይታዩት የመንገድና ትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች በሥርዓት እግረኛውንና ተሽከርካሪውን ሲያስተናግዱ እና ትራፊኮችም በክት ልብሳቸው ደምቀው ሥራቸውን ሲያከናውኑ ነበር የሰነበቱት። እኔ ግን ይህንን ስመለከት በአእምሮዬ የሚመላለሰው «እስከመቼ የሚዘልቅ ይሆንየሚለው ጥያቄ ነበር።

እርግጥ ነው ይህ መደረጉ ለእንግዶቻችን የሀገራችንን መልካም ገጽታ ያሳይልናል። ለእኛ ለነዋሪዎቿ ደግሞ አዲስ አበባ ራሷን ሸውዳ ለታይታ የቀረበች ከተማ መሆኗን ያስረዳናል። ይህ አባባል ትክክል አይደለም የሚል ካለ፤ ሰሞኑን ትጉህ የነበሩትን ትራፊኮቻችንን እና ሥርዓት የያዙትን ጎዳናዎቻችንን ከቀናትና ሳምንታት በኋላ ይመልከት። ለራሳችን ክብር የምንሰጥ ከሆነ ይህ ይቀጥላል፤ ካልሆነ ግን ልማዳችን ያገረሽብንና ጥንቅር ይበልብን።

 

ብርሃን ፈይሳ

 

Published in መዝናኛ

ሰዎችን ማልማት ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው። መንግሥትም ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራ ይገኛል። በዚህም በሀገሪቷ ያለው የትምህርት ተደራሽነት ላይ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። በሦስት ትውልዶች የተከፋፈሉ 34 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተከፍተው የተማረ የሰው ኃይል የማፍራት ተልዕኳቸውን በመወጣት ላይ ናቸው። በተጨማሪም11 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች በግንባታ ላይ ናቸው። በሥራ ላይ ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የአርሲ ዩኒቨርሲቲ በ2007.ም ነው ሥራ የጀመረው። ዩኒቨርሲቲው በመደበኛና በርቀት መርሀ ግብሮች 2959 ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል። ለዛሬም ከዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ከዶክተር ሂርጶ ጤኖተሺቴ ጋር በነበረን ቆይታ፤ በዩኒቨርሲቲው ስላለው የመማር ማስተማር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርገናል። ሙሉ ቃለ ምልልሱን እነሆ!

አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ በማህበረሰብ አገልግሎት፣ በቴክኖሎጂ ስርፀትና ምርምሮች ምን ዓይነት ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ነው?

ዶክተር ሂርጶ፡- ዩኒቨርሲቲው እንደ ማንኛውም ዩኒቨርሲቲ መማር ማስተማር፤ የምርምር ሥራ፤ የማህበረሰብ አገልግሎት የሚሉ ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮችን ይዞ ነው የሚሰራው። ዩኒቨርሲቲው ምን ላይ ነው ልቆ መገኘት ያለበት በማለት ለመለየት ተሞክሯል። በዚህም የማህበረሰብ ጤና መጠበቅ፤ አርሲ የሚታወቀው በስንዴና በገብስ ምርት በመሆኑ ግብርናውን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አሠራሮችን ለማሻሻል እየሰራን እንገኛለን። ዩኒቨርሲቲያችን መሪ ሃሳብ (ሞቶ) «እንደ ከዋክብት አትሌቶቻችን ሊቅ ባለሙያዎችን እናፈራለን» ብለን ነው የተነሳነው። ስፖርትንም አንድ የለውጥ ማዕከል አድርጎ በመውሰድ ለስፖርት ዘርፍ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን።

ለዚህ ዓላማ መሳካት በስፖርት ልምድና የተሻለ የትምህርት ዝግጅት ያላቸውን ሰዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ አምጥተናል። በአገር ውስጥ እንዲሁም እንድ ኮርያና ቤልጂየም ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ቅንጅት ለመፍጠር እየሰራን ነው። በመማር ማስተማሩ ሂደት በቅድመ ምረቃ እና ድህረ ምረቃ መርሀግብሮች በመደበኛ፣ በተከታታይ የትምህርት ክፍሎች እያስተማርን ነው። ስለዚህ መሪ ሃሳቡን ዕውን ለማድረግ ግብዓቶችን የማሟላት፤ መጽሐፍት ቤቶችን በሁለቱም ፕሮግራሞች ማደራጀት፣ ለዩኒቨርሲቲው የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችን ለመዘርጋት 52 ሚሊዮን ብር በመመደብ እየሰራን ነው። የምርምር ውጤቶች ለትምህርት ግብአት እንዲሆኑ የማድረግ፤ «የሚሰሩ ምርምሮች ለዕድገት» የሚል አስተሳሰብ በመያዝ የሚሰሩ የምርምር ውጤቶች አነስተኛ የገቢ ምንጭ ላላቸው ዜጎች ላይ ያተኮሩ እንዲሆኑ አድርገናል።

አዲስ ዘመን፡- ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚወጡ የምርምር ሥራዎች ኅብረተሰቡን የሚጠቅሙ እንዲሆኑ ይጠበቃል። በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው ምን ያህል ውጤታማ ሥራ ሰርቷል?

ዶክተር ሂርጶ፡- ከዚህ ቀደም የሚሰሩ የምርምር ሥራዎች ሼልፍ ላይ ነበር የሚቀመጡት። አሁን ግን ከዚህ መውጣት አለብን በማለት የምርምር ሥራዎቻችን እታች ወርደው ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ አስበን እየሰራን ነው። በዩኒቨርሲቲው ከተሰሩና እየተሰሩ ካሉ ሥራዎች መካከል ለመጥቀስ የዓይን ህክምና አንዱ ነው። 80በመቶ የሚሆነው የዓይን ህመም በህክምና ሊድን የሚችል ነው። በዚህም ጥናት በማድረግ እዚህ መጥተው አገልግሎት ማግኘት ለማይችሉ ባለሙያዎች ቦታው ድረስ በመሄድ የነፃ ዓይን ህክምና አገልግሎት ሰጥተናል። ችግር ያለባቸውን ቦታዎች በመለየትም ሶላር መነፅር የማደል፤ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር ግንኙነት በመፍጠር ለአካባቢው የሚሆን የስንዴ ምርጥ ዘር በመለየት ሞዴል ለተባሉ አርሶአደሮች የማደል ሥራ ተሰርቷል። ቀጣይም እነዚህ አርሶአደሮች ደግሞ ለሌሎች የሚያሰራጩበት እንዲሆን ታስቦ በመሰራቱ ውጤታማ ሆነናል ።

አዲስ ዘመን፡- የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘቡና የተመረጡ የምርምር ሥራዎች ተግባራዊ የተደረገባቸው ቦታዎች ምን ዓይነት ተጨባጭ ውጤት ተገኘ?

ዶክተር ሂርጶ ፡- በከተማው ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ላይ ያተኮረ ጥናት፤ በጤና ዘርፍ ከምግብ እጥረት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመለየትና መፍትሔ በማፈላለግ፤ በሕፃናት ላይ፤ በእናቶች የቅድመ ወሊድ ክትትል በተመለከተ፤ የአይረን እጥረት ያለባቸውን ልጆች የመለየትና ቀጣይ የመድኃኒቶች ድጋፍ ለማድረግ እና ለማከፋፈል ዝግጅት ጨርሰናል። በተጨማሪም ችግሮችን በየዲፓርትመንቶች በመለየት መፍትሔዎቹን ታሳቢ አድርገን እየሰራን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው ሴቶችን ከመደገፍና ከማብቃት አንፃር ምን ያህል ውጤት አመጣ?

ዶክተር ሂርጶ፡- በዩኒቨርሲቲው የሴቶች ተሳትፎ ሁለት በመቶ ብቻ ነበር። ያንን በአስተዳደር ከተወያየን በኋላም ባለፈው ዓመት ብቻ 30 ሴቶች እንዲቀጠሩ በማድረግ ተሳትፎውን ወደ 14 በመቶ ከፍ ማድረግ ችለናል። በቀጣይም ቅጥር ሲፈፀምም ሆነ ዝውውር ሲደረግ ለሴቶች ቅድሚያ ለመስጠት ዕቅድ ይዘናል። ባሎቻቸው ሌላ ቦታ የሆኑትን ሠራተኞች ወደዚህ በማቅረብም ሴቶች ሥራቸው ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው። ሴቶችን ሳይዙ መሮጥ በአንድ እግር እንደ መሮጥ ስለሚቆጠር የሴቶችን ተሳትፎ 50 በመቶ ለማድረስ እየሰራን ነው። ነገር ግን ሴቶችን ወደ አመራር ለማምጣት ስናነጋግራቸው የተለያዩ ማህበራዊ ሰበቦችን በማስቀመጥ ከኃላፊነት የመሸሽ ነገሮች ይስተዋላሉ። ስለዚህ ይህ አመለካከት በሴቶች በኩል ሊቀረፍ እንደሚገባ እናምናለን።

በአቅም ደረጃ ስናይ ከዚህ ቀደም ወደ አመራርነት ከመጡት ውስጥ በሥርዓተ ፆታ ቢሮ ላይ ትሰራ የነበረችው የተሻለ ተሳትፎ ነበራት፤ የምርምር ሥራዎችንም ትሰራ ነበር። በዚህ ዓመት ወደ ረዳት ፕሮፌሰርነት ካሳደግናቸው ውስጥ አንዷ ናት። ለፒ ኤች ዲ ትምህርትም ውጭ ሀገር እንድትሄድ አድርገናል። ሌሎች እርሷን መሳይ እንዲፈጠሩ ለማድረግ በትምህርታቸው እንዲጠናከሩ ድጋፍ እያደረግን ነው። ምንም እንኳ አንድ ሰው ወደ ትምህርት ለመግባት ሁለት ዓመት አገልግሎት ቢጠይቅም እኛ በአስተዳደር በማየት ለሁለት ሴቶች ቅድሚያ በመስጠት ትምህርታ ቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።

አዲስ ዘመን፡- በዩኒቨርሲቲዎች ከሦስቱ ፕሬዚዳንቶች ቢያንስ አንዷ ሴት መሆን እንዳለባት ግብ ተቀምጧል። አሁን በምን ደረጃ ላይ ናችሁ?

ዶክተር ሂርጶ፡- ከሦስቱ ፕሬዚዳንቶች አንዷ ሴት መሆን አለባት በሚለው ሃሳብ ተስማምተናል። ወደ አመራር ከመጡት ውስጥ ወንድና ሴት እኩል ቢመጣ ለሴቶች ቅድሚያ እንሰጣለን። የሴቶች ቁጥርም አናሳ የነበረ በመሆኑ ክፍተቶች ነበሩ። በዩኒቨርሲቲያችን ውስጥ በሦስተኛ ዲግሪ ደረጃ ያለች አንድ ሴት ብቻ ናት። እንደ ዩኒቨርሲቲ ግን በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመስራት ሴቶችን እያበቃን ክትትል እያደረግንና እየደገፍን መሄድ ላይ አስበንበታል።

ትምህርት ላይ ያሉትን ሴቶችንም የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጣቸው ነው። በአስተዳደር ደረጃ በማየትም በዝውውር ሴት ሠራተኞችን እያመጣን ነው። ነገር ግን ወደ አመራርነት ለማምጣት አንድ ሰው አንድ ዓመት አንድ ቦታ ላይ ማገልገል አለበት የሚል መመሪያ ስላለ እሱን እየጠበቅን ነው።

አዲስ ዘመን፡- አካል ጉዳተኞችን በመደገፍ ረገድ ምን የሚጠቀስ ሥራ ሰርታችኋል?

ዶክተር ሂርጶ፡- ከአካል ጉዳተኞች ጋር ተያይዞም ጋሪ ገዝተን የአካል ድጋፍ እንዲያገኙ አድርገናል። በሁሉም የትምህርት ክፍሎች የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን ተማሪዎችም በመለየት የኮፒና የሳሙና ድጋፍ እያደረግን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲውን ምቹና ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲኖር ለማድረግ ምን እየሰራችሁ ነው?

ዶክተር ሂርጶ፡-ሴኩላሪዝም ላይ ያተኮረ ሥልጠና ለመምህራንና ተማሪዎች ተሰቷል። በተለይ ተማሪዎች በጋራ እንዲወያዩ ተደርጓል። አስተማሪዎችም የትምህርት ክፍለጊዜ እንዳይቀሩ ተወያይተን መግባባት ላይ ደርሰናል። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ተማሪዎች የፀብ መነሻ መምህራን ሳያስተምሩ ሲቀሩ «እየተማርን አይደለንም» የሚል ቅሬታ ነው። ስለዚህ ከአስተዳደር አንድ አንድ ሰው ተመድቦ ክፍል ኦዲት ያደርጋል። እያንዳንዱ ቀን ምን ያህል ክፍለ ጊዜ አለ? ስንቱን በትክክል ተምረዋል? በሚል ሪፖርት ይቀርባል።

ችግር ያለባቸው 11 መምህራን የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል። ከአስተዳደሩ ጋር ችግር የሚፈጥሩና ለመማር ማስተማሩ ሰላማዊ መሆን እንቅፋት የሚሆኑትን በዲሲፕሊን ኮሚቴም የቀረቡ አሉ። በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የተነሳበትን ዓላማ ስኬት ለማድረግና እና ለዕቅዶቻችን መሳካት ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና መንግሥት ጋር በጋራ በመሆን እንሰራለን።

አዲስ ዘመን፡- ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ሆነው መረጃዎችን ስላካፈሉን እናመሰግናለን!

ዶክተር ሂርጶ ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

 

ፍዮሪ ተወልደ

 

 

Published in ማህበራዊ

 

ጥብቅ እና የተፈፃሚነትን ብቃት ከሚፈታተኑ የዓለማችንም ሆነ የአገራችን ተግዳሮቶች አንዱ ሙስና ነው፡፡ መረጃና ማስረጃ የሚባሉ ጉዳዮች አስቸጋሪዎች ናቸው፤ መረጃውን ማግኘት ቢቻል ማስረጃውን ማግኘት ከባድ ፈተና ነው፡፡ በተለይ በከፍተኛ ባለሥልጣኖች ላይ ማስረጃ ማሰባሰብና ማደራጀት የአገሪቱን ሕግና የየመንግሥታቱን፣ የመቆጣጠርና የማስፈፀም ብቃት የሚፈታተን ነው፡፡ በሙስና ውስጥ የሚዘፈቁት ደግሞ ከላይ ከአገሪቱ መሪዎች አንስቶ በየደረጃው የሚገኙ ባለሥልጣኖች ናቸው፡፡ የሕዝብ ገንዘብ ይዘርፋሉ፣ ማስረጃ ያጠፋሉ፣ ጥቂት መሪዎችን ለማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ አሊ አብደላ ሳላህ የየመን ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ በአረብ ፀደይ አብዮት ሥልጣን እስከለቀቁበት ድረስ የመዘበሩት የሕዝብ ሀብት 60 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ቤን አሊ የቱኒዚያ መሪ ነበሩ፡፡ በአረብ አብዮት በ2011 ሥልጣን ለቅቀው ከአገር ሲወጡ ግምቱ 21 ሚሊዮን ዶላር የሆነ ወርቅና አልማዝ ከቤታቸው ተገኝቷል፡፡

ሆስኒ ሙባረክ የግብጽ መሪ በ2011 ከሥልጣን እስከወረዱበት ጊዜ ድረስ «ቤተመንግሥቴን አድሳለሁ» በሚል ሰበብ 17 ሚሊዮን ዶላር መዝብረዋል፤ ሞቡቱ ሰሴሴኮ ከማርች 1997 የዛየር (የአሁኗ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ) ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ሎዛን (ፈረንሳይ) ውስጥ ባለ 30 ክፍል የተንጣለለ ቪላ በ5ነጥብ5 ሚሊዮን ዶላር ገዝተዋል፡፡ የመዘበሩት ገንዘብ 5 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ሳኒ አባቻ ከ1993- 1998 የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ 5 ቢሊዮን ዶላር መዝብረዋል፡፡ መንግሥት 450 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሀብትና ንብረታቸውን ወርሶባቸዋል፡፡ ያህያ ጃሜ ለ22 ዓመታት የጋምቢያ ፕሬዚዳንት ነበሩ በምርጫ ተሸንፈው ሥልጣን ለማስረከብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በዙሪያቸው ባሉ አገራት መሪዎችና በሴኔጋል ጦር ሠራዊት ጣልቃ ገብነት ሥልጣናቸውን ለቅቀው ወደ ጊኒ ሲሄዱ በመንግሥት ካዝና የነበረውን 11 ሚሊዮን ዶላር መዝብረዋል፡፡ ከ13 በላይ የከፍተኛ ዋጋ የቅንጦት መኪኖች ሲኖራቸው ሁለት ሮልስ ሮይስ የተባሉና አንድ ቢትሌ የሚባል በድምሩ ሦስት መኪኖችን ጭነው ይዘው ሄደዋል፡፡ የተቀሩት አሥር መኪኖች እንዲጫኑላቸው ትዕዛዝ ሰጥተው ነው የሄዱት ይጫኑ/ አይጫኑ የተባለ ነገር የለም፡፡

የኢንዶኔዥያው መሪ ሱሀርግቶ ከ1967-1988 የነበሩ መሪ ናቸው። 35 ቢሊዮን ዶላር መዝብረዋል። የተከሰሱት ግን በ570ሚሊዮን ዶላር የተጭበረበረ የበጎ አድራጎት ገንዘብ ምክንያት ብቻ ነው፡፡ የፊሊፒንስ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፈርዲናንድ ማርቆስ ከ1965-1986 በዘለቀው የሥልጣን ቆይታቸው 10 ቢሊዮን ዶላር መዝብረዋል፤ መንግሥት ባደረገው ጥረት በስዊስ ባንክ ከተቀመጠው የምዝበራ ገንዘብ ማስመለስ የቻለው 700 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ ማስረጃ የተገኘው ለዚሁ መጠን ብቻ ስለሆነ ባለቤታቸው ኤሜልዳ ማርቆስ ከፍተኛ ደረጃና ዋጋ ያላቸው 3000 በታዋቂ ዲዛይነር የተሰሩ ጫማዎች እንደነበራቸው ይታወቃል፡፡

እነዚህ ምሳሌዎች የሚያሳዩት መረጃ ቢኖርም ማስረጃ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ነው፡፡ እነዚህ የሙስና ምዝበራዎች ማስረጃ አጥተው የቀሩት በራሱ በሙስናው ኃይለኝነት ነው፡፡ ሙስናን ለመዋጋት ብንዘምት ሙስናው ራሱ ባለ በሌለ ኃይሉ በእኛ ላይ ይዘምትብናል፡፡ ማስረጃ የሚሆኑ ሰዎችንና ሰነዶችን ለማጥፋት ያለ ርህራሄ ውጊያ ይከፍትብናል፡፡ እነኝህን ምሳሌዎች የተገነዘበ ማንኛውም ሰው «ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ርምጃ ያልተወሰደው ማስረጃ ስላልተገኘ ነው» በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሰጡትን መግለጫ እውነተኝነት ለማመን አይቸገርም፡፡ እነዚህ በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ የማጋበስ ተግባራት «ሙስና» የሚለው ቃል ከሚገልፀው በላይ ናቸው፡፡

አገር ዘረፉ… ካዝና ገለበጡ… ወዘተ ወይም ሌላ ከባድ ቃል መግለጫ ሊገኝላቸው ይገባል፡፡ ከዚህ ዓይን ያወጣ የዘረፋ አካሄድ ውጪ የሙስና አንዱ ምንጭ የታላላቅ ፕሮጀክቶችን ሥራዎች አፈፃፀም ማጓተት ነው፡፡ በሙስና ለመክበር ከተፈለገ ሥራዎችን ከማጓተት የተሻለ ብልሀት የለም። ስለ ማጓተት ከተነሳ የሰሞኑ ትኩስ ወሬ ስለሆነው ስለ ሩሲያ ስታዲየም ሥራ ማጓተት ጉዳይ ጥቂት ማለት አለብን፡፡ ሩሲያ ቅዱስ ፒተስበርግ (st.Pitterburg) ውስጥ ክሬስቶቭስኪ ወይም ዜኒት አሬና የተባለ የእግር ኳስ ሜዳ (ስታዲየም) እየገነባች ነው፡፡ የምንነጋገረው ስለ ሥራ ማጓተት መሆኑን አንዘንጋ! የስታዲየሙ ሥራ የተጀመረው በ2007 ሲሆን ይጠናቀቃል ተብሎ የተያዘለት ጊዜ በ2011 ነበር፡፡ የተመደበለት በጀት 6ነጥብ7 ቢሊዮን ሩብል (110 ሚሊዮን ዶላር) እስካሁን አልተጠናቀቀም አሥር ዓመት ፈጅቷል። አሁን ወጪው 48 ቢሊዮን ሩብል (800 ሚሊዮን ዶላር) ሆኗል፡፡

ፊፋ (FiFA) 2018 የዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎችን ያካሂድበታል ተብሎ የሚጠበቅ ነው ያውም መጠናቀቅ ከቻለ! ጋዜጠኞች እያብጠለጠሉት ነው፡፡ የተለያየ ቅጽል ስም አውጥተውለታል። (unfinishable bottomless pit… UwM/useless waste of Money…) ይሉታል ማለቂያ የሌለው … የገንዘብ ጎርፍ ቢለቁበት የማይሞላ ቀዳዳ በርሜል፣… ዋጋቢስ የገንዘብ ብክነት ከልክ በላይ የተጓተተና ከበጀት በላይ የሆነ ( massively late & over budget) እየተባለ ይተቻል፡፡ በአራት ዓመት ውስጥ ያልቃል ተብሎ 110 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት ፕሮጀከት በአሥራ አንድ ዓመቱና በ800 ሚሊዮን ዶላር ማለቅ ካልቻለ ታዲያ ምን ሊባል ይችላል ለስታዲየሙ ግንባታ የሚውለው ግብአት ብረት የግንባታ ማሽነሪ ቴክኖሎጂና የሙያተኞች ክህሎትና ከፍተኛ ልምድና ገንዘብ ያላት አገር ሆና ሳለ ይህን ያህል መጓተት ምን ይባላል? የሙስና ሴራ/ሥራ ሳይኖርበት እንደማይቀር መረጃዎች አሉ፡፡ ማስረጃ ግን የለም፡፡

በእኛ አገር ሁኔታ ከመሬትና ከጉልበት ሌላ ምንም ሳይኖረን ሁሉን ነገር ከውጭ እያስመጣን እየሰራን 6 ወርና ዓመት ከተጓተተ ራሳችንን ይዘን ለመጮህ ይቃጣናል፡፡ ዋናው ነገር መረጃና ማስረጃን የሚያጣጥምና መረጃው ለማስረጃው መጋቢ (ደጋፊ) እንዲሆን የሚያስችል ጠንካራ ሕግና ብቃት ያለው የማስፈፀም አቅምን የሚያረጋግጥ ቁመና ሊኖረን ይገባል፡፡ ማስረጃ የለም ተብሎ ሙሰኞች እንደልባ ቸው የሚሆኑበት ሁኔታ መፈጠር የለበትም ሕጉ ይጠበቅ !

ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ

የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን።

 

ግርማ ለማ

 

 

Published in ፖለቲካ

የመንግሥት ተቋማት ያለመናበብ ዜጎችን ለፍትሕ እጦት ዳርጓል፤

 

በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ሰንጋተራ አካባቢ ወረዳ ዘጠኝ በቀድሞው ቀበሌ 53 ተገኝቻለሁ። ቦታው ከስምንት ዓመታት በፊት የነበረበትን ሁኔታ ለሚያውቅ ዛሬ ያለበትን ሁኔታ ለመገመት ይቸገራል። ቀድሞ የነበሩ የተጎሳቆሉ መኖሪያዎች አሁን በሚያማምሩ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተተክተዋል።

አካባቢው በመልሶ ማልማት ከተለወጡት አካባቢዎች አንዱ መሆኑ ለሁሉም ደስታን ያጭራል። በኑሮ ሂደት ነውና ሁልጊዜም በለውጦች መሀል የሚፈጠሩ መዘበራረቆች ይኖራሉ። አንዱ ደስታን ሲጎናፀፍ ሌላው ደግሞ በኀዘን ድባብ ሊዋጥ ይችላል። በመጣው ለውጥ እየተገረምኩ ብዙም ርቀት ሳልሄድ ግንባታ ባልተከናወነ ባቸው ቦታዎች ላይ በላስቲክ ተጠልለው የሚኖሩ ግለሰቦችን ተመለከትኩ። ሰብሰብ ብለው ሱሶቻቸውን በማስተናገድ ላይ ያሉ ወጣቶችም ቁጭ ብለዋል።

እግሮቼ በአካባቢው ወዳለ አንድ የፈራረሰ ቤት አመሩ። በቦታው ሦስት ወጣቶች ቁጭ ብለዋል። በቤቱ የሚኖሩ ወጣቶች ነበሩ። ከመሀከላቸው አንዱ ወጣት ነብዩ አባተ የቤት ቁጥር 520 ባለቤት እንደሆነ ነገረኝ። ከ1956 .ም ጀምሮ የተገበረበትን ደረሰኝ አውጥቶ አሳየኝ። አያቱ ፊትአውራሪ ከተማ አየለ የነበራቸውን ማስረጃዎችም በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የተሰጣቸውንም ካርታ አሳየኝ። ከመረጃዎቹ መካከል አንዱ የቀበሌው (በቀድሞ አጠራር) ማህበራዊ ፍርድ ቤት በወቅቱ ለነበረው ሥራና ከተማ ልማት ቢሮ የፃፈው ደብዳቤ ነው።

ቤቱ ከአዋጅ 47/67 በፊት የተሰራና ምንም ዓይነት ኪራይ ቀመስ ቤት የሌለ መሆኑንም በ5/2/1992 .ም በዋለው ችሎት በምስክሮች ማረጋገጡን ይገልፃል። ወጣቱ ልማቱን እንደሚደግፍና ለዚያም ቪላ ቤታቸውን እንዳፈረሱ አስታውሷል። «በወቅቱም እንደማንኛውም የግል ቤት አፍርስን ፍራሹንም በ14 ሺህ አራት መቶ ብር ገዝተንም ነበር። ካሳችን እና ግምታችን ተለጥፎ ውሰዱ ተብለንም ተስተናግደን ነበር» ይላል። በስተመጨረሻ ግን ወረዳው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ቤቱ የእኔ ነው ማለቱን ገለፀልን ሲል በወቅቱ የነበረውን ሂደት ይናገራል። ብንመላለስም ምላሽ ማግኘት ባለመቻላችን እስካሁን ድረስ እዚህ እንገኛለን ሲል ቅሬታውን ኀዘን በተቀላቀለበት ስሜት ይገልፃል።

ወጣት ነብዩ እንደሚናገረው በወቅቱ ቤቱ ሲፈርስ እናለማለን ብለው 350 ካሬ ቦታ ወሎ ሰፈር ምትክ ተሰጥቷቸው ነበር። «የሚመለከታቸውን አካላት ሄደን ስናናግር ይህ የመንግሥት ተቋም ነው አይዋሽም እዚያው ጨርሱ የሚል ምላሽ ነው የተሰጠን» በማለት ይናገራል።

ኤጀንሲውንም ለመክሰስ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፣ ፍትህ ሚኒስቴር፣ እንባ ጠባቂ ቢሄዱም እንኳ ምላሽ የሰጣቸው አካል እንዳልነበር ይገልፃል። ነብዩ ቀጠለ «ኤጀንሲው የእኔ ነው ካለ ሊያስተዳድረው ይገባል። ሲያስተዳድረው ደግሞ ደረሰኝ ይቆርጣል። አልያም ትርፍ ቤት ሆኖ በአዋጁ ሊወርሰው ይገባል። ነገር ግን ይህ ሁሉ ባልሆነበት ሁኔታ ነው መጀመሪያ ሙሉ በሙሉ የእኔ ነው ሲል የቆየው። ከዚያ ደግሞ ሃሳቡን ቀይሮ ልክ እንደ አንድ ተወላጅ ግማሹ ቤት የእኔ ነው ብሎ የተነሳው» ብሏል።

ከዚህ በላይ ግን የሚሰማቸው አካል በማጣታቸው ያላቸውንም ጥሪት በመጨረሳቸው በግማሹ መስማማታ ቸውን ይገልፃል። በፈራረሰው ቤት ውስጥ 12 ቤተሰብ እንደሚኖሩና ከዚያም ውስጥ አንደኛዋ እህታቸው አካል ጉዳተኛ በመሆኗ በአሁን ሰዓት እንደተቸገሩ ይናገራል። ቦታው ለሌቦች አመቺ እና ለሕይወት አስጊ በመሆኑ የተወሰኑት የቤተሰብ አባላት ቤት ተከራይተው እንደወጡም አስታውሷል። የተረፈው ዕቃቸውንም በመጠበቅ ቁጭ ብለው ያድራሉ። «ሳንፈልግ ያልሆነ ሕይወት ውስጥ ገብተናል» በማለት ነው ብሶቱን የሚናገረው።

በመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ አዲስ እጅጉ እንደሚገልፁት «መንግሥት ማግኘት ያለበትን ጥቅም ሳያገኝ መቅረት የለበትም። የቤቱን ታሪክ ማየት ተገቢ ነው» ይላሉ። ቤቱን የቀድሞ ባለንብረት የሆኑት ፊትአውራሪ ከተማ ይዞታ ነበር። ቆይቶም ለርሳቸው ልጆች እንዳወረሱ ቅድመ አዋጅ የነበረ ታሪክ ነው። ቤቱ በሆነ ወቅትም ኤጀንሲው ወይም በወቅቱ አጠራር ኪራይ ቤቶች በአዋጅ 47/67 የተወረሰ መሆኑን የሚያሳይ ፋይል እንዳለ ገልጸዋል። አዋጁ በ1967 .ም ትርፍ ቤት የሆኑትን ወደ መንግሥት እንዲገቡና መንግሥት እንዲያስተዳድራቸው ያደረገ አዋጅ ነው። ነገር ግን በተለያዩ ጊዜያት የወረስነው ቤት በመሆኑ ሊወረስብን አይገባም በማለት የቀረቡ ጥያቄዎች ነበሩ።

ከሁለቱ ወራሾች መካከል አንደኛው ወገን ሌላ ትርፍ ቤት ያለው መሆኑ ስለታወቀ ግን በአዋጁ መሠረት ተወርሶ በወቅቱ ኪራይ ቤቶች እንዲያስተዳድረው እንደተደረገ ያስታውሳሉ። ከ1969እስከ 1970 ባለው ጊዜም አንድ የውጭ ሀገር ዜግነት ያለው ግለሰብም በ229 ብር ከሃምሳ ሳንቲም ተከራይቶት እንደነበርም የሚያሳይ መረጃ አላቸው። ከዚያ በኋላም ለቀበሌ ጽሕፈት ቤትነት ሲያገለግል ቆይቷል። ቀበሌው ከዚያ ሲወጣ ግን በምን አግባብ ወደ ሰዎቹ እንደተላለፈ የጠራ መረጃ አለመኖሩን ነው ያስታወሱት። በአንድ በኩል ደግሞ በሆነ ወቅት ኤጀንሲው ሲያስተዳድረው እንደነበር የሚያሳይ ፋይል አላቸው።

«2003 .ም አካባቢ ቦታው ለልማት ሲፈለግ ክፍለ ከተማው ኤጀንሲውን ማረጋገጫ ጠይቋል። በተሰጠውም መረጃ ሲጣራ ግማሹን ቤት ኤጀንሲው ሲያስተዳድረው እንደነበረ የሚያስረዳ መረጃ አያይዘን ለክፍለ ከተማው ልከናል» በማለት አቶ አዲስ ይናገራሉ። 2006 ላይ ልጆቹ ግማሹን ኤጀንሲው ይውሰድ ብለው የስምምነት ደብዳቤ አስገብተዋል። ኤጀንሲውም አካውንት ቁጥሩን በመግለፅ ገቢ እንዲደረግለት ለክፍለ ከተማው ደብዳቤ እንደፃፈ ያለው መረጃ ያሳያል ይላሉ።

ኪራይ ቀመስ በመሆኑ በወቅቱ አጠራር ኪራይ ቤቶች በ1960ዎቹ መጨረሻ በአዋጅ እንደወረሰ ቢናገሩም፤ ግለሰቦቹ ጋር ደግሞ በ5/2/1992 .ም ኪራይ ቀመስ ቤት አለመኖሩ ተገልፆ የተፃፈ ደብዳቤ ተገኝቷል። ሁለቱ ሃሳብ ይጋጫልና ለምን? የሚል ጥያቄ አነሳሁላቸው። አቶ አዲስ የተባለው መረጃ በኤጀንሲው እንደሚገኝ አረጋገጡልኝ። በወቅቱ አጠራር ክፍለ ሀገሩ በአሁኑ አጠራር ከተማ አስተዳደሩ ለቀበሌ ይሰጠኝ ብሎ ኤጀንሲውን የጠየቀበት ደብዳቤም እንዳለ ይጠቁማሉ። ሲለቅ ግን ሰዎቹ በምን አግባብ እንደገቡ የሚገልፅ መረጃ ግን እንዳላገኙ ይናገራሉ።

ሌላው ያለን ነባራዊ ሁኔታ ቤትና መሬት እንድንረሳ አያደርገንም። ነገር ግን ኤጀንሲው ቤቱን ረስቶት ቆይቶ ወይስ ሌላ ምክንያት አለው ከእነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ ቤቱን ያስታወሰው ያውም ቤቱ የእኔ ነው ያለውም በመልሶ ማልማት ሂደቱ መሆኑ ግር ቢያሰኝም ላቀረብኩላቸው ጥያቄም አቶ አዲስ በወቅቱ ከነበረው የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ጋር ተያይዞ ችግር እንደነበር ያስቀምጣሉ። የኤጀንሲው ክትትል ማድረግ ክፍተት ምክንያት ግን መንግሥት ሊያገኝ የሚገባውን ነገር ሳያገኝ መቅረት እንደሌለበት ጠቁመዋል።

ቀጣይ የእነዚህ ሰዎች ዕጣ ፈንታም የሁለቱ የጋራ ስምምነት ላይ መሠረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ሁለታችንም ግማሹን ስለሆነ የምንፈልገው በዚህ መሠረት መጨረስ እንደሚችሉ ይናገራሉ። ይህ አያስማማኝም የሚሉ ከሆነም ወደ ሕግ መሄድ ይችላሉ ብለዋል። በሌላ ወገን ስናይ ደግሞ በቅርቡ ከክፍለ ከተማው መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት መፍትሔ ይሰጣቸው ተብሎ መጥተው እንደነበር ወጣት ነብዩ አስታውሷል። ነገር ግን ቤቱ ስለፈረሰ «በፈረሰ ቤት ላይ መብት መፍጠር አንችልም» ብለውናል ሲል ይናገራል። ምን ማድረግ እንዳለብንም ስንጠይቅ «ያፈረሰውን አካል ሂዱና እሱ ምላሽ ይስጣችሁ» ተብለናል በማለት ይገልፃል። መንግሥት ችግራችንን አይቶ ምላሽ እንዲሰጠን እንፈልጋለን፤ ፍትህ እንሻለን በማለት ይናገራል።

ወደሌላኛው የፈረሰ ቤት መንገዴን ቀጠልኩ ወይዘሮ አባይነሽ በቀለ የተባሉ ዕድሜያቸው 58 የሆነ መተዳደሪያቸውን ጠላ መሸጥ ያደረጉ እናት አገኘሁ። ባለፉት 54 ዓመታት በአካባቢው ኖረዋል። ቦታው ለልማት በመፈለጉ የልማት ተነሺ መሆናቸውን ይናገራሉ። ልማት አስፈላጊ እንደሆነም ያምናሉ። «ሁሉም ሰው ምላሽ አግኝቶ ሲሄድ እኛ ግን ዛሬም እዚህ በላስቲክ ቤት እንገኛለን። እህቴ በክርክር ላይ እያለችም ሕይወቷ አልፎ እዚሁ ነው የቀበርኳት» የሚሉት ወይዘሮ አባይነሽ፤ የቤት ቁጥር 273 ላይ ነዋሪ ነበሩ። የቤት ቁጥሩ በሦስት ህዝባር የተለያየ እንደነበር አስታውሰው 75 ካሬ ለሦስት ውሰዱ ተብለናል ሲሉ ተናግረዋል። «ተስማምታችሁ ኑ» ብሎ ክፍለ ከተማው እንደነገራቸውም አስታውሰዋል፡፡

በልደታ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈትቤት የሚመለከታቸውን አካላት ለማነጋገር ሄድኩ፡፡ ምንም እንኳን ዕለቱ መንግሥት ለባለጉዳይ መስተንግዶ ያስቀመጠው ቀን ቢሆንም ለረጅም ሰዓታት ኃላፊው ጋር ገበተው ያልወጡት የተቋሙ ሠራተኞች ውስጥ ሆነው ሳቃቸው ይሰማል፡፡ ቁጭ ብዬ ያሳለፍኩት ጊዜ ቢረዝምብኝ ጸሐፊዋን ባለጉዳይ እንዳለ ለኃላፊው እንድታሳውቀው ነገርኳት፡፡ እርሷም ፈገግ በማለት «እዚህ ቢሮ ስትመጪ መጀመሪያሽ ነውበማለት ጥያቄዬን በጥያቄ መለሰችልኝ፡፡

ኃላፊው ጋር ለመግባት ከሚጠብቁ ባለጉዳዮች መካከል ወይዘሮ ትዕግስት ወልደ ዮሐንስና አሸናፊ ወልደዮሐንስ በቢሮው ለሦስት ዓመታት እንደተመላለሱ ነገሩኝ፡፡ ከሁለት ወራት ወዲህ ቢያንስ ሰሚ ጆሮ አግኝተናል፡፡ ቀደም ብሎማ የሚያስተናግደንም አልነበረም ይላሉ፡፡

ተራዬ ደርሶ እኔም ወደቢሮው ዘለቅኩ፡፡ መረጃው እንዲመጣ ለሠራተኞች ቢነገራቸውም «መረጃው እየተፈለገ ነው» በማለት ለረጅም ሰዓታት ቆየሁ፡፡ በቢሮው ሌላ ባለጉዳይ ገቡ፡፡ ሁለት ሠራተኞችን ኃላፊውን በማስጠራት «ለምን ለባለጉዳይ በጊዜውና በአግባቡ መስተንግዶ አትሰጡምበማለት ተናገራቸው፡፡ ከዚህ በኋላም ከተግባራቸው ተስተካክለው ካልተገኙ የእርምት እርምጃ እንደሚወስድ ገለጸ፡፡ እኔም መረጃውን እንዲሰጠኝ ወደ ተመራሁት ሰው ቀጠልኩ፡፡

አቶ አሸናፊ ከፋ በልደታ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንትና የከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ናቸው፡፡ «አብዛኛው ፕሮጀክት የተጠናቀቀው ከ2006 .ም በፊት ነው፡፡ በዚህም የአካባቢው ተነሺዎች በወቅቱ ማግኘት ያለባቸውን አግኝተው እንዲስተናገዱ ተደርጓል፡፡ በተለያዩ ምክንቶች መረጃ ባለማሟላትና ስምምነት ባለመፍጠር ግን ያልተስተናገዱ አሉ፡፡ የተጠቀሰውም ቤት ቁጥር እኛ እምናውቃቸው በአንድ ሰው ነው፡፡ በዚህም 75 ካሬ እንዲወስዱ ነግረናቸዋል» በማለት ነበር ጉዳዩ በምን ደረጃላይ እንዳለ የተናገሩት።

ለቀጣይ ሥራዎች የተሻለ ከተማ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት አንድ ሳሎን እንዲሁም መኝታ ቤት መስራት የሚቻልበት ሁኔታ ለመፍጠር 75 ካሬ ይሰጣል፡፡ ይህ ትንሹ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ግን ሊስተናገዱ ያልቻሉት መስማማት ባለመቻላቸው ነው፡፡ ይዞታው አንድ በመሆኑ አንድ ምትክ ነው የሚሰጣቸው በማለት ይገልፃሉ፡፡ በመመሪያው መሠረት ካሳ ለየብቻ ነው የሚያገኙት በዚህም ካሳው በተከፈተው አካውንት ውስጥ ገብቷላቸዋል። ሰዎቹ ተስማምተው በመጡ ጊዜም ወጪ ተደርጎ ይሰጣቸዋል።

እንደ አቶ አሸናፊ ገለፃ፤ መሬቱም ማስፋፊያ ቦታ ላይ ተጠይቆ ተለክቶ ይዞታው በእነርሱ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ ስለዚህ ተስማምተው በመጡበት ሰዓት መስተናገድ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

«መረጃ በማጥራት የወሰዱ ጊዜያቶች አሉ፡፡ በመመሪያው መሠረት ባለይዞታን ለማስተናገድ ካርታ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ነገር ግን እነርሱን ለመርዳት በማሰብ በአሁን ወቅት ቤቱ ባይኖርም እንኳን እነዚህ ሰዎች ካርታ ባይኖራቸውም ሕጋዊነት አላቸው የሚለውን በማየት በፕሮሰስ ካውንስል አስወስነንላቸዋል፡፡ ወደኋላ በመሄድ ባጣራነውና ባገኘነው መረጃ ትክክለኛ በመሆኑ ቤቱ በአካል ቢኖር መብት ሊፈጠርለት እንደሚችል ታሳቢ አድርገን ነው እንዲስተናገዱ ያደረግነው» በማለት የሄዱበትን የአሠራር ርቀት አስታውሰዋል፡፡

በመልሶ ማልማት መመሪያው አንድ ሰው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሳይኖረው መብት ሊፈጠርለት እንደማይችል ይናገራሉ፡፡

በክፍለ ከተማው ላይ ግን ሁለት ዓይነት አሠራር ሲሰራ ይስተዋላል፡፡ በአንድ በኩል ተመሳሳይ መረጃ ያላቸው በቤት ቁጥር 520 ይኖሩ የነበሩት የቤተሰብ አባላት ልማቱን ለማገዝ ካላቸው ፍላጎት ቪላ ቤታቸውን አፍርሰዋል፡፡ ብዙ ውጣ ውረዶችንም አሳልፈው ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ጋር በግማሽ ይገባኛል ቢስማሙም ከክፍለ ከተማው ግን «በፈረሰ ቤት ላይ መብት ልንፈጥርላችሁ አንችልም» የሚል መልስ በማግኘታቸው ከተከበረው መኖሪያ ቤታቸው ወጥተው ሜዳ ላይ ፍርስራሽ ውስጥ ሕይወትን ይገፋሉ፡፡

ክፍለ ከተማው በፈረሰ ቤት መብት መፍጠር አንችልም ብሎ ምላሽ ቢሰጣቸውም በሌላ በኩል ደግሞ ለቤት ቁጥር 273 በፈረሰ ቤት ላይ በፕሮሰስ ካውንስል በማስወሰን ቤቱ ቢፈርስም በታሳቢ ተብሎ መብት እንደተፈጠረ አቶ አሸናፊ ከሰጡን መረጃ መረዳት እንችላለን፡፡

ምናልባት ይህን መሰል የአሠራር ወጣ ገባነት ስንመለከት የፍትሃዊነት ጥያቄን እንድናሰብ ያስገድደናል። ሁለቱም ግን በአንድ ክፍለ ከተማ ከዚያም አልፎ በተመሳሳይ መኖሪያ አካባቢ የተከናወኑ መሆናቸውን ስናይ ምን ያህል ዥንጉርጉር አሠራር እንዳለ ያመላክታል፡፡ በመሆኑም ፍትህ የሚሰፍነው ሁሉንም ሰዎች በአኩል በማስተናገድ ነውና የሚመለከታቸው አካላት ክፍተቱን በማየት አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት ይገባቸዋል።

 

ፍዮሪ ተወልደ

 

 

Published in ፖለቲካ

2001.ም ጀምሮ እስከ 2008 .ም ድረስ የቡና የወጪ ንግድ ላይ ማጣራት ተደርጓል፤

 

የግብርና ምርት ግብይት ላይ በየዓመቱ የተለያዩ ይዘት ያላቸው የሕግ ጥሰቶች ይፈጸማሉ። በተለይም ከገዢና ሻጭ ፍላጎቶች ጋር በሚያያዝ ጉዳዮች የግብይት ውሎች ይፈርሳሉ። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን የሚከታተላቸው የግብይት ሂደቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥሰቶች ወደ ሕግ ጉዳይ ከመሄዳቸው አስቀድሞ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር የመከላከል አሠራር ይከተላል። በዚህም በሻጭ በኩል በቂ ምርት ስለመኖሩ ማረጋገጫ ይወሰዳል። በተረካቢ በኩል ደግሞ ምርቱን ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ በባንክ ስለመኖሩ ማረጋገጫ ይጠይቃል።

ይህም ሆኖ የግብይት ውሎች በመፍረሳቸው ምክንያት ግብይቶች ላይከናወኑ የሚችሉበት ዕድል ያጋጥማል። በዚህም ወቅት ጉዳዩ በሕግ እንዲፈታ በተቋሙ ስር በሚገኘው ፍርድ ቤት ለመፍታት ጥረት ይደረጋል። ከባለሥልጣኑ አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮች ካጋጠሙ ደግሞ ለሚመለከተው አካል ያስተላልፋል። ባለሥልጣኑ ይህን እና አጠቃላይ የግብይት ችግሮችን በተመለከተ የሕግ ጥሰቶች መከሰታቸውን ማረጋገጥ እና የእርምት እርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት ተጥሎበታል።

በቅርቡ ከምርት ግብይት ጋር የተያያዘ ለ8 ዓመታት የተፈጸሙ የሕግ ጥሰቶች መኖራቸው ታውቋል። ይህም በተቋሙ የሕግ ክፍል ሊስተናገዱ የማይችሉ በመሆናቸው ጉዳዩ በተለያዩ የሕግ ተቋማት እየታዩ ይገኛል። በዚህም ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በተደረገ ማጣራት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ እና የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት የታቀደለት የቡና ምርት በላኪዎች አማካኝነት ወደ ውጭ አገር አለመላኩን ማረጋገጥ ተችሏል። ምርቱ በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ተልኮ አይሸጥ እንጂ ላኪዎቹ ላይ በተደረገው ማጣራት መዳረሻው የት እንደሆነ ለማወቅ እንደሚቻል ነው ባለሥልጣኑ ያሳወቀው።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ኦሌሮ ኡፒየው እንደሚናገሩት፤ ባለፉት 8 ዓመታት ውስጥ ወደውጭ ከተላከው እና የተገኘው ገቢ መረጃ በመንግሥት ተቋማት እየተፈተሸ ይገኛል። በተለይም ወደ ውጭ ለመላክ ታስቦ ያልተላከውን መጠን እና ላኪዎቹን የመለየት ሥራ ተከናውኗል። በዚህም 54 ላኪዎች ቡናን ወደ ዓለም ገበያ በሕጋዊ መንገድ ቀረጥ ከፍለው ስለማስተላለፋቸው ጥርጣሬ መኖሩን እና በመረጃ መረጋገጥ እንደሚገባው ታምኖበታል። በዚህም መሠረት ለዓለም ገበያ መቅረብ የነበረበት19 ሺ ቶን ቡና በአገር ውስጥ ተሸጧል ወይም በኮንትሮባንድ መንገድ ወደ ሌሎች አገራት ሊሸጥ እንደቻለ ነው ሂደቱ የሚያሳየው። ይህም አገሪቷ ማግኘት የነበረባትን 76 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያሳጣ ተግባር ሆኗል። ይህን ያህል ሀብት ቀርቶ የአንድ ዶላር ምርትም ለውጭ ገበያ ነው ተብሎ ከቀረበ በአገር ውስጥ ገበያ ሊሸጥ አይገባም። በመሆኑም ችግሩን ማን ፈጠረው? እንዲሁም የቡናው መዳረሻ የት ነበር? ለሚለውን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ማጣራቶች እየተደረጉ ይገኛል።

በዚህ መሰሉ ተግባር ላይ በዋናነት ተሳትፈዋል የተባሉ 24 ላኪዎች በቡና ግብይት ላይ እንዳይሳተፉ በንግድ ሚኒስቴር በኩል እገዳ ተጥሎባቸው ነበር። ይህም የተደረገው ላኪዎቹ ቡናውን ለየትኛው አካል እንዳስተላለፉት እና ተጠያቂዎችን እስኪያቀርቡ ድረስ ነበር። በመሆኑም የሚፈለግባቸውን መረጃ እና ግዴታቸውን የተወጡ ድርጅቶችም በዚህ አግባብ ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል። በዚህም መሠረት ወደ አስር የሚጠጉት ድርጅቶች እገዳቸው እንዲነሳ እየተደረገ ይገኛል። ይህም ገበያውን ለማረጋጋት ታስቦ የተደረገ ጭምር ነው።

«ይሁንና ወደ ሥራ እንዲገቡ የተደረጉ ላኪዎች በሕግ የተመሰረተባቸው ክስ ይቋረጣል ማለት ባለመሆኑ በሥራ ላይ እያሉ ጉዳያቸው በሕግ መታየቱን የሚቀጥል ይሆናል» በማለት ነው ኢንጂነር ኦሌሮ የሚናገሩት። በሌላ በኩል በማጣራቱ ሂደት በቂ መረጃ ያልተገኘባቸው እና በመረጃ ስህተት ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ የተደረጉ አራት ድርጅቶች ይገኛሉ።

እንደ ኢንጂነር ኦሌሮ ገለጻ ከሆነ፤ እያንዳንዱ ሻጭ እና ተረካቢ ምርት እና ገንዘብ የተለዋወጡበትን የሚጠቁም መረጃ በንግድ ሚኒስቴር በኩል እየተመዘገበ ይቀመጣል። በመሆኑም ጥፋቱ መፈጸሙ የተረጋገጠው ከ2001.ም ጀምሮ እስከ 2008 .ም ድረስ የተደረገው የወጪ ንግድ ላይ ማጣራት ተደርጎ ነው። በመሆኑም ማንኛውም አካል በየትኛውም ጊዜ ሕገወጥ ተግባር ፈጽሞ ማምለጥ እንደማይችል ያሳየ ክስተት አድርጎ ማየት ይቻላል። ይሁንና የተከሰተው ችግር በቀጣይ ጊዜያት የሚደረገውን የዘርፉ ግብይት ላይ የሚደረገውን ማጣራት በየወቅቱ ማከናወን እንደሚገባ ትምህርት የሚሰጥ ነው።

«ተጨማሪ ማጣራቶች ቢደረጉ ሌሎችም የሕግ ጥሰቶችን የፈጸሙ አካላት ሊገኙ ይችላሉ» የሚሉት ደግሞ በባለስልጣኑ የህግ ጉዳዮች ክትትልና ምክር አገልግሎት የስራ ሂደት መሪ የሆኑት አቶ ይርሳው ዘውዴ ናቸው። በተለይም ችግሩ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽእኖ ሲታሰብ ጉዳዩ ቀላል እንዳልነበር መገመት ይቻላል። በመሆኑም አሁንም ተመሳሳይ የሕግ ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ የሚደረገው ቁጥጥር እና ክትትል ጠንካራ መሆን እንደሚገባው ነው የሚጠቁሙት። ጥፋት ፈጽመው የተገኙ አካላትም ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ተገቢ በመሆኑ የፍትህ ሂደቱ በተደራጀ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል። ይህንንም ክትትል ቡና ላይ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የወጪ ንግድ ምርቶች ላይ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይም ለዘርፉ ሕገወጥ ተግባር መስፋፋት አስተዋጽኦ የሚያበረክተውን ኮንትሮባንድ መቆጣጠር ተገቢ ነው። ለዚህም የኮንትሮባንድ አሠራሩን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተቀናጀ ሁኔታ መከላከል ይገባል። ይህም በዘርፉ የሚታየው የገቢ መጓደል የሚያስቀር ብቻ ሳይሆን የጥራት ችገሮችን የሚቀርፍ ጭምር ነው።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ እንደሚናገሩት፤ ወደ ውጭ አገራት እንዲያቀርቡ የተመደበላቸውን ቡና በአገር ውስጥ የሸጡ ላኪዎች አሉ። ይህ ስህተት ቢሆንም በሌላ በኩል በአገር ውስጥ ያለው የቡና ዋጋ እና ገበያ ማደጉን ያሳያል። ማንም አካል ቢሆን ኪሳራ ውስጥ ገብቶ ምርቱን መሸጥ የሚፈልግ ነጋዴ አይኖርም። በዚህም አግባብ ለአገር ውስጥ የቀረበው ቡና ከውጭው ጋር ሲነፃጸር የተሻለ ገቢ እንዳስገኘ መገመት ይቻላል። ይህም የአገር ውስጥ ፍላጎት ማደጉን እና የገዢው ኅብረተሰብ አቅም ማደጉን ያሳያል። የሕዝቡን አቅም ማደግ እንደ በጎ የልማት ግብ ማየት ቢቻልም ይህ ውጤት በወጪ ንግዱ ላይ የሚያዘናጋ ጉዳይ መፍጠር እንደማይኖርበት ይታመናል። በመሆኑም በቡና ንግድ ላይ ሕገወጥ ተግባር የፈጸሙ አካላትን ለማጋለጥ ከፌዴራል ፖሊስ አባላት ጋር በጋራ እየተሰራ ነው።

«የወጪ ንግዱን የሚጎዳ ተግባር ሲፈጸም ላኪዎች ብቻቸውን ሊያደርጉት አይችሉም የሚል እምነት አለ» የሚሉት አቶ ሳኒ፤ ሕገወጥ ተግባሩን ከመንግሥት ተቋማት ባለሙያዎች እና አመራሮች ጋር በጋራ ሊፈጽሙት እንደሚችሉ ያላቸውን ጥርጣሬ ይገልፃሉ። ይህን ለማጣራትም አስፈላጊው መረጃ እየተሰባሰበ ይገኛል።

የባለስልጣኑ የኢኮኖሚ ትንተና የስራ ሂደት መሪ ዳይሬክተር አቶ ኡርጌሳ ባይሳ በበኩላቸው፤ ችግሩ ተከሰተ በተባለበት ከ2001 .ም እስከ 2008 .ም ድረስ በሕጋዊ መንገድ ለዓለም ገበያ የተላከው የቡና ምርት ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን መሆኑን ነው የሚያስረዱት። ከዚህ አሃዝ ጋር የት እንደደረሰ ያልታወቀውን 19ሺ ቶን ቡና ጋር ማነጻጸር ከተቻለ አንድ በመቶ እንኳን የማይሞላ ነው። ይሁንና በንፅፅር መጠኑ አነስተኛ ነው በሚል ዝቅተኛ ግምት የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልሆነ ነው የሚያስረዱት። በመሆኑም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በመንግሥት ደረጃ አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ ይገኛል። ችግሩ የሰፋ ሊሆን ይችላል በሚልም ጥናት እየተካሄደ በመሆኑ ማጣራቱ ሲጠናቀቅ በቀጣይ አስፈላጊውን መረጃ ለሕዝብ ማድረስ ይቻላል። ይህም በዘርፉ የሚከሰቱ ጉድለቶችን ተከታትሎ ለመቀነስ የሚረዳ አካሄድ ነው። ከመንግሥት ተቋማት በተጨማሪም ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በዘርፉ የሚታዩ ሕገወጥ ተግባሮችን እና አሠራሮችን በመለየት ለሚመለከተው አካል የማሳወቅ ልማዱን ሊያዳብር ይገባል። ይህም በዋናነትም ሕገወጦችን አጋልጦ የወጪ ንግዱን ለማጠናከር ያግዛል። በዚህም የአገሪቷን ገቢ በማሳደግ ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ እድገቱን ማስቀጠል ይቻላል።

 

ጌትነት ተስፋማርያም

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።