Items filtered by date: Tuesday, 07 February 2017

በዓለም ላይ ውድ ከሚባሉና ቅንጡ ስፖርቶች አንዱ የሆነው የጎልፍ ስፖርት በ15ተኛው ክፍል ዘመን በኔዘርላንድ እንደተጀመረ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ስለ ጎልፍ ስፖርት ሲነሳ ከስፖርቱ ጀርባ ስማቸው አብሮ ከሚነሱ ተጫዋቾች መካከል ታይገር ውድስና ግሬግ ኖርማንን በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።

የጎልፍ ስፖርት ከሌሎች ስፖርቶች ለየት ከሚያደርጉት ባህሪያት መካከል ውድድሩን ለማካሄድ የሚጠይቀው ቦታ እጅግ ሰፊ መሆኑ ቀዳሚው ሆኖ የሚነሳ ሲሆን፤ይህ ሰፊ ቦታን የመፈለግ ችግርም በተለይ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥርና የመሬት እጥረት ችግር በሚስተዋልባቸው አገራት ከፍተኛ ራስ ምታት ሲሆን ይስተዋላል።ለዚህ ጥሩ ማሳያ የምትሆነው አገር ደግሞ ቻይና ናት።

የጎልፍ ስፖርትና ውድድሩ የሚፈልገውን ሰፊ የመሬት ጥያቄን የቻይናን እሳቤ በሚመለከት፤የሰሞኑ የዴይሊ ቻይና ዘገባ እንዳመላከተው ከሆነም እ..አ በ1949 የቻይና ህዝባዊት ሪፐብሊክ መስራች ማኦ ዜዱንግ የጎልፍ ስፖርት ከሚጠይቀው የቦታ ስፋት አንፃር አስፈላጊ አለመሆኑን በማመን ስፖርቱን ከአገሪቱ በማገድ ቀዳሚው ሰው ናቸው።

ማኦ በወቅቱም አንድና ብቸኛ የሆነውን የሻንጋይ የጎልፍ መጫወቻ ሜዳ በመዝጋት ወደ የእንስሳት ማቆያ ፓርክነት ያስቀየሩ ሲሆን ከዚህ ጊዜ ጀምሮም በተለይ በአገሪቱ ከዓመት ዓመት እያደገ ከመጣው የህዝብ ቁጥርና የከተማ መጨናነቅ ጋር ተዳምሮ ለረጅም ጊዜያት ስፖርቱን በመደገፍና በመቃወም መሃል ስትወዛገብ ቆይታለች።

ይህን ተከትሎ በተለይ የመሬት እጥረት እጅግ ከባድ እየሆነ በመጣበትና የሪል ስቴት ቤቶች ዋጋ ጣራ በነካበት በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የጎልፍ ሜዳዎች ሰፊ ቦታን መያዝ አልዋጥ እያላት መጥቷል።

የሰሞኑ አሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ እንዳመላከተው ከሆነ ታዲያ፤ ቻይናና የጎልፍ መጫወቻ ሜዳዎች አለመዋ ደዳቸው በተግባር መታየት ጀምሯል።አገሪቱም ለጎርፍ መጫወቻ ሜዳነት የሚያገለግሉ ሰፋፊ ቦታዎችንና በሜዳው ላይ የሚገኙ የውሃ ሀብቷን ለሌላ ግልጋሎት ለመጠቀምና ለዚህም፤111 የሚጠጉ የጎልፍ መጫወቻ ሜዳዎችን ለመዝጋት ከውሳኔ ላይ ደርሳለች።እንደ ዢንዋ ዘገባ ከሆነ ደግሞ አገሪቱ ተጨማሪ 65 የሚሆኑ የጎልፍ መጫወቻዎችን ለመዝጋት ፍላጎት አላት።

ምንም እንኳን ልክ እንደ እግር ኳስና ቅርጫት ኳስ ሁሉ የአገሪቱ መንግሥት አገር በቀል የጎልፍ ተጫዋቾችን ለማፍራት ከውጭ አገር አሰልጣኞችን በማምጣት መዋዕለ ንዋዩን እያፈሰሰና ስፖርቱን እያበረታታ ቢሆንም፤ ባለሃብቶች በጎልፍ ሜዳ ሰበብ የሚይዙት ሰፋፊ ቦታዎች ግን ገደብ ይኖራቸው ያለች ትመስላለች።

አገሪቱ ከዚህ ቀደም እ..አ በ 2004 አዳዲስ የጎልፍ መጫወቻ ሜዳዎች ግንባታ ላይ ማዕቀብ መጣሏ የሚታወስ ሲሆን፣ በወቅቱ የመጫወቻ ሜዳዎቹ ከ200 አይበልጡም ነበር። ይሁንና የማዕቀቡ ተፈፃሚነት እምብዛም ጠንከር ያለ ባለመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት የጎልፍ መጫወቻ ሜዳዎቹ እያደር ቁጥራቸው በማሻቀብ በ2004 ከነበረው በሦስት እጥፍ በማደግ አሁን ላይ ወደ 683 ከፍ ብለዋል።

እንደ ዢንዋ ዘገባ ከሆነ፤ባለሃብቶች የጎልፍ መጫወቻ ሜዳዎቹን በፓርክ ወይም በሌላ ፕሮጀክት ሽፋን የሚገነባቸው ሲሆን፤ ‹‹የህዝብ ስፖርት ፓርክ›› በሚል ሽፋን የተገነቡ ህገ ወጥ የጎልፍ መጫወቻ ሜዳዎች መኖራቸውም ታውቋል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የጎልፍ ስፖርት በቻይና እጅግ አወዛጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ጭምር ሲነሳ የሚደመጥ ሲሆን፤የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ በሚመራው የፀረ ሙስና ዘመቻ ምርመራ ውስጥ የገባ የስፖርት ዓይነት ነው። ከዚህ በተጓዳኝ የቻይና ኮምዩኒስት ፓርቲ መርህ የጎልፍ ስፖርትን መጫወት እንደአባካኝነት የሚቆጠር ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት በ2015 ፓርቲው 88 የሚሆኑ አባላቱ ጎልፍ እንዳይጫወቱ ማገዱም የሚታወስ ነው።

አስናቀ ፀጋዬ


Published in ስፖርት

 

የአፍሪካ ቼስ ሻምፒዮና በመጋቢት ወር 2009 ዓም፤ በጅማ ከተማ አስተናጋጅነት ይካሄዳል። 4ነጥብ2 በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ይህ ውድድር ከ13 ያላነሱ የኮንፌዴሬሽኑን አባል ሃገራት ያሳትፋል ።

ውድድሩን አስመልክቶ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ፣ውድድሩ በኢትዮጵያ ሲዘጋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል ፡፡ ውድድሩ ስፖርቱን ለማስፋፋት መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡ በውድድሩ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከተጋበዙት ሃገራት አብዛኛዎቹ እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል ፡፡የተቀሩትም በቀጣዮቹ ጊዜያት ይሁንታቸውን ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። ተሳታፊ ሃገራቱ በአምስት ሴትና በአምስት ወንዶች የሚወከሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ አስተናጋጅ ሃገር በመሆኗ ሰባት ወንድና ሰባት ሴት ተጫዋቾችን የምታካፍል ይሆናል። በውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑ ተጫዋቾች የገንዘብና የማዕረግ ሽልማት ይበረከትላቸዋል ፡፡ በዓለም የቼስ ሻምፒዮና ላይ አፍሪካን ወክለው የመሳተፍ እድልም ያገኛሉ።

ኢትዮጵያ በቼስ ስፖርት ያላትን ደረጃ ለማሳደግ፣ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማዘጋጀት ልምድ ለማግኘት፣ በወጣቶች ዘንድ የቼስ ስፖርትን ንቅናቄ ለመፍጠር፣ ውድድሩ የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንን ሽፋን የሚያገኝ በመሆኑ የሃገሪቷን መልካም ገጽታ ለማሳየት እንዲሁም የጅማ ከተማ ያላትን ባህልና መስህቦቿን ለማስተዋወቅ የሚረዳ መሆኑም ተገልጿል።

ውድድሩ የሚካሄደው የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን ከኦሮሚያ ክልልና ከጅማ ከተማ ቼስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ሲሆን፤ለውድድሩ አስፈላጊ የሚሆነውን ገንዘብም ከተለያዩ አካላት በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኝ የጅማ ከተማ ቼስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ በቀለ ገልጸዋል። ጅማ ይህንን እድል ማግኘቷ ከፍተኛ ደስታ የሚፈጥር መሆኑን አቶተሾመ ጠቁመው፤ የከተማው አስተዳደር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ኮሚቴዎችን አደራጅቶ ዝግጅት በማድረግ ላይ የሚገኝ መሆኑን አስረድተዋል።

 

ብርሃን ፈይሳPublished in ስፖርት

በውድድሩ መጀመሪያ ላይ የቀበሌ መታወቂያ ጉዳይ ብዙ ውዝግብ አስነስቷል፤

 

በአዲስ አበባ ከተማ ዳገታማና ጫካ በሚባዛባቸው ቦታዎች ሩጫን የሙጢኝ ብለው ሀገራቸውንና ራሳቸውን ለማስጠራት በልምምድ የተጠመዱ የከተማዋ አትሌቶች በርካታ ናቸው፡፡ በአትሌቲክስ ስፖርት ትልቅ ደረጃ መድረስን ዓላማ አድርገው ቀንና ሌሊት በልምምድ የተጠመዱት እነዚህ አትሌቶች የሰሩትን ልምምድና ያደረጉትን ዝግጅት በተለያዩ ከተማና አገር አቀፍና የውድድር መድረኮች ላይ ይፈትሻሉ፡፡

እነዚህ አትሌቶች በከተማም ይሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ ውድድሮች በጭራሽ እንዲያ መልጣቸው አይፈልጉም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ውድድሮቹ ወቅታዊ አቋማቸውን የሚገመግሙባቸው የአቋም መለኪያቸው መሆኑ ነው፡፡ በተለይ ማራቶንን አማራጭ ያደረጉ አትሌቶች በዓመት ውስጥ ከአንድና ከሁለት ጊዜ በላይ የማይካሄደውን የማራቶን ውድድር በጉጉት ይጠብቃሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሞሃ ለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ ጋር ባለው አብሮ የመስራት ስምምነት በዓመት ውስጥ በተለያዩ ርቀቶች በርካታ ውድድሮችን እንደሚያካሂድ ይታወቃል፡፡ ፌዴሬሽኑ በዓመቱ ውስጥ ከሚያካሂዳቸው ውድድሮች ውስጥ አንዱ የሆነው የፔፕሲ ማራቶን ውድድር ከትናንት በስቲያ ተካሂዷል፡፡ መነሻውንና መድረሻውን ሰሚት አካባቢ ባደረገውና ለ21ኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ የፔፕሲ ማራቶን ውድድር ላይ ክለብ ያላቸው ክለባቸውን ወክለው የሌላቸውም በግላቸው ተሳትፈዋል፡፡

በየዓመቱ ከ200 በላይ አትሌቶች በሚሳተፉበት በዚህ የማራቶን ውድድር ላይ አሸናፊዎቹ ከሚያገኙት የገንዘብ ሽልማት ባሻገር ለተሳታፊዎቹ የሚሰጣቸው የምስክር ወረቀት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው በውድድሩ ላይ የተሳተፉ አትሌቶች ይናገራሉ፡፡

በዘንድሮው ውድድር ላይ 99 ወንዶችና 33 ሴቶች በድምሩ 132 ሯጮች ክለቦቻቸውን ወክለው ረጅሙን ርቀት ሮጠዋል፡፡ 72 ወንዶችና 8 ሴቶች ደግሞ በግል የርቀቱ ተካፋዮች ሆነዋል፡፡ 21 ኪሎ ሜትር በሸፈነውና አንጋፋ ሯጮች በተሳተፉበት ውድድር ላይም 21 የጤና ሯጮች የእለቱን ሙቀት ተቋቁመው ውድድራቸውን አካሂደዋል።

ከሩጫው ቀን ቀደም ብሎ ተሳታፊ አትሌቶችን መዝግቦ የመሮጫ ቁጥር የሰጠው የአዲስ አበባ አትሌቲከስ ፌዴሬሽን፣ለሩጫው እውን መሆን የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችንም በማከናወን መተዳደሪያ ደንቡን መሰረት አድርጎ በዘንድሮው ውድድር ላይ 202 ወንዶችና ሴቶችን መዝግቦ ነበር 42 ኪሎ ሜትር ከ195 ሜትር የሚሸፍነውን ውድድር እሁድ ማለዳ ያዘጋጀው።

ይሁንና ከውድድሩ መጀመር አስቅድሞ ፌዴሬሽኑ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች መታወቂያቸውንና የተሰጣቸውን የምዝገባ ቁጥር እንዲያሳዩ ጠየቀ፡፡ በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ የቅድመ ምዝገባውን አጠናቀው በእለቱ የተሰጣቸውን ቁጥርና መታወቂያ የያዙ እውቅና ተሰጥቷቸው ተሰለፉ፡፡ መታወቂያ ያልያዙ ነገር ግን የተሰጣቸውን ቁጥር የያዙ መሳተፍ እንደማይችሉ በአዘጋጆቹ ሲገለጽ ቅሬታዎች ይሰሙ ጀመር፡፡ የፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች በሃሳበቸው ጸንተው ሁለቱንም ያላሟሉ መሳተፍ እንደሌለባቸው ቢገልጹም ጥቂት አትሌቶች ሩጫው ከሚያመልጠን በሚል ውድድሩን ሲጨረሱ መረጃቸውን ለማምጣት ረጅሙን ርቀት ጀመሩት፡፡

ሰዓታትና ርቀቱ እየገፋ ሲሄድ አሸናፊዎች በጉጉት ሲጠበቁ ታደሰ አሰፋ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ቀዳሚ ሆኖ ገባ፡፡ እርሱን በመከተል ዓለማየሁ መኮንን ከኤልሚ ኤሎንዶ ሁለተኛ፣ በላቸው ዓለሙ ከፌዴራል ፖሊስ ሶስተኛ እንዲሁም አማኑኤል ተሾመ በግል አራተኛ ደረጃን ይዘው ርቀቱን ጨረሱ፡፡

ይሁን እንጂ ውድድሩን በሁለተኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ዓለማየሁ መኮንን የቀበሌ መታወቂያውን ባለመያዙ ያስመዘገበው ውጤት እንደማይያዝለት ተነገረው፡፡ በጉዳዩ ግራ የተጋባው አትሌት ዓለማየሁ እምባ በተሞላ ዓይኑ ምሬቱን ቢገልጽም «በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት በሩጫው ላይ ለመሳተፍ የሚያስችል መስፈርት አላሟላህም ስለዚህ የሮጥከው ዋጋ የለውም» የሚል ምላሽ ተሰጠው፡፡ ፌዴሬሽኑ ከውድድሩ በኋላ አሸናፊዎችን ሲሸልም ታደሰ አሰፋን በአንደኝነት፣ በላቸው ዓለሙን በሁለተኝነት እንዲሁም አማኑዔል ተሾመን በሶስተኛነት እውቅና ሰጥቶ የገንዘብና የሜዳሊያ ሽልማት አበረከተ።

በዚህ ውድድር ላይ ሁለተኛ ሆኖ ውድድሩን ካጠናቀቀው በተጨማሪ15ኛ ሆኖ የጨረሰው ኢሳያስ ዳታ፣26ኛ ሆኖ የጨረሰው ሰሳዲቅ ምስጋና፣ 28ኛ ሆኖ የጨረሰው አማረ ምንአየው ሌሎች ውጤታቸው የተሰረዘባቸው አትሌቶች ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውድድሩን ከማካሄዱ ቀደም ብሎ የቀበሌ መታወቂያ ጠይቆ ተሳታፊዎችን ቢመዘግብም ውድድሩን ከማስጀመሩ በፊት መታወቂያ ያልያዙትን መከታተል ላይ መጠነኛ ክፍተት ያለበት ይመስላል፡፡

ዓመት ሙሉ ሰፊ ዝግጅት ያደረጉና በነርሱ አገላለጽ መታወቂያ ይዘው እንዲመጡ ያልተነገራቸው እነዚህ ሯጮች አቋማቸውን ለመፈተሽ ረጅሙን ርቀት ቢያጠናቅቁም ያሰቡት የተሳትፎ ደብዳቤ የውሃ ሽታ ሆኖባቸዋል፡፡ ሩጫውን በሁለተኝነት ያጠናቀቀው የኤልሚ ኤሎንዶ ክለብ ሯጩ ዓለማየሁ መኮንን መታወቂያ ባለመያዙ ያስመዘገበው ውጤት ተሰርዞ ሶስተኛ ለወጣው አማኑኤል ተሾመ መሰጠቱን ሲያረጋግጥ ዓይኖቹ በእምባ ሲሞሉ ለማስተዋል ችለናል፡፡

የተፈጠረውን ችግር እንዲያስረዱን ከጠየቅናቸው ውስጥ አንዱ የሆነው ኢሳያስ ዳታ «ፌዴሬሽኑ ምዝገባውን ያካሄደበት ዋና ምክንያት ሯጮችን ህጋዊ ለማድረግ ነበር፡፡ የመወዳደሪያ ቁጥሩን ስገዛ መታወቂያ አሳይቼ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ቁጥሩን ስገዛ በሩጫው ቀን መታወቂያ ይዘህና የሚል ትዕዛዝ አልሰጡኝም›› በማለት ይገልጻል፡፡

ኢሳያስ የተሰጠውን ቁጥር ብቻ ይዞ መወዳደር እንደማይችል ይገለጽታል፡፡ ልፋቱ መና ከሚቀር ብሎ ባለቤቱ መታወቂያ እንድታመጣለት አድርጎ ነው ሩጫውን ያካሄደው፡፡ ሩጫውን ጨርሶ መታወቂያውን ቢያሳይም የገባበት ሰዓት እውቅና ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ‹‹እንግዲህ ለማን አቤት ይባላል፡፡ ቢያንስ አሳማኝ ምክንያት ሊሰጡን ይገባል፡፡» በማለት በምሬት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ሳዲቅ ምስጋናውም ተመሳሳይ እጣ ደርሶበታል፡፡ «ማንነትህን የሚገልጽ መታወቂያ አሳይ ሲሉኝ መታወቂያ የለኝም፣ የፓስፖርቴን ፎቶ በስልኬ ላይ አንስቼዋለሁ፤ እዩትና ፍቀዱልኝ፡፡ በኋላ መታወቂያዬን አምጥቼ ታረጋግጣላችሁ ብዬ ብለምናቸው አሻፈረኝ አሉ›› ሲል በወቅቱ መግለጹን ያብራራል፡፡ስመዘገብ በውድድሩ እለት መታወቂያ ይዘህ ና እንዳልተባለም ነው የሚናገረው ፡፡

‹‹ስለ ውድድሩ ደንብ በደንብ ግንዛቤ ሳያስጨብጡን መቅጣታቸው ያሳዝናል›› ያለው ሳድቅ በየ5 ኪሎ ሜትሩ ምልክት እየተደረገ መሮጡንም ነው የሚናገረው፡፡ የውድድሩ አጠቃላይ ምስል መቀረጹንም ጠቅሶ ምስሉን በማየት ችግራቸው በአፋጣኝ ታይቶ ምላሽ እንዲሰ ጣቸውም ነው የጠየቀው።

አዲስ ዘመን ጋዜጣ የአትሌቶቹን ቅሬታ መሰረት በማድረግ የጋዜጣው ሪፖርተር የፌዴሬሽኑን ባለሙያዎች አነጋግሯል፡፡ ባለሙያዎቹ በሰጡት ማብራሪያ የዓለም አቀፉን ህግና የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብን መሰረት አድርገው መስራታቸውን ተናግረዋል፡፡ ማራቶን ረጅም ርቀት የሚሸፍን ውድድር መሆኑን ጠቅሰው፣በርካታ ህገ ወጥ ድርጊቶች የሚበዙበት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ የተነሳም የትኛውም ተሳታፊ ማንነቱን የሚያሳይ መታወቂያ ሳይዝ መወዳደር እንደማይችል በግልጽ መቀመጡን አመላክተዋል፡፡

በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ቢሆን መስፈርቱን ሳያሟላ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የመጣን አትሌት ጎትቶ ማውጣት እንደማይቻል ጠቅሰው፣ በፔፕሲው ውድድር ላይም በተመሳሳይ መስፈርቱን ሳያሟሉ የሮጡ አትሌቶችን ከማቋረጥ ይልቅ ውጤታቸውን ለመሰረዝ መገደዳቸውን ነው ያስታወቁት፡፡ በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት ትናንት በተደጋጋሚ ወደ ፌዴሬሽኑ ስልክ ብንደውልም ሊያነሱልን ፍቃደኛ አልሆኑም ፡፡

 

ታምራት አበራPublished in ስፖርት
Tuesday, 07 February 2017 19:26

የንብ ነገር

ንቦች በማራቸው የሰው ልጅን የሚያስደስቱትን ያህል በአያያዝ አለማወቅ ሳቢያም ጉዳት ሲያደርሱበት ከብዙ ገዳዩም ሲያስተጓጉሉት መመልከት የተለመደ ነው ፡፡ በአገራችን ንቦች ወደ ቤት ሲገቡ እንግዳ እንደሚመጣ በማሰብ በፀጋ የሚቀበሉ እንዳሉ ሁሉ ለማባረር ወይም ለመሸሽ የሚሞክሩም ብዙ ናቸው ፡፡

ሰሞኑን ለንባብ የበቃ የዩፒ መረጃ እንዳመ ለከተው የንብ መንጋ በደቡብ አፍሪካና በሲሪላንካ መካከል ሊካሄድ ነበረው የክሪኬት ግጥሚያ እንዲዘገይ ምክንያት ሆኗል ፡፡ የንብ መንጋው ወደመጫወቻ ሜዳው በመግባቱ ተጫዋቾቹ ከንቦቹ ለመሸሽ ተገደዋል፡፡ ሜዳውን የሚያፀዱ ባለሙያዎች ንቦቹን ከሜዳው ለማስለቀቅ የተለያዩ መድኃኒቶችን፣ ሰፕሬይና የእሳት ማጥፊያ አስከመጠቀምም ደርሰዋል ፣ እንዲያም ሆኖ ግን ንቦቹ ወይ ፍንክች በማለታቸው ጨዋታው ለአንድ ሰዓት ያህል ጊዜ መዘግየት የግድ ሆኖበታል፡፡ አናቢዎች መጥተውም ነው ንቦቹን በመሰብሰብና በፕላስቲክ ሳጥን በማድረግ ሜዳውን ለጨዋታው ክፍት ያደረጉት ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በእንግሊዝ ሀገር እንደ ሆስፒታል ኮርኒስን ቀፎዋቸው ያደረጉ 100 ሺ የሚጠጉ ንቦች የሰሩት ማር ሆስፒታል ውስጥ እየተንጠባጠበ በማስቸገሩ የተነሳ ንቦቹ በአናቢዎች ተይዘው ወደ ሌላ ቦታ እንዲዘዋወሩ ተደርጓል፡፡

የዛፍ ላይ ንቦች ማህበር ያሰራጨው ፎቶ እንደሚያሳየው፤ ካርዲፍ ከሚገኘው ሮክ ሁድ ከተባለው ሆስፒታል ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወር የተደረገው የንብ መንጋ በእዚህ ስፍራ ለአምስት ዓመታት ቆይቷል ፡፡

የንብ መንጋውን የንብ አናቢ ባለሙያዎች መጋዝ በመጠቀም ንቦቹን ከኮርኒሱ እንዲሁም ከሰሩት ቀፎ እንዲወጡ በማድረግ ወደ ተዘጋጀላቸው ቦታ ወስደዋቸዋል ፡፡አስናቀ ጸጋዬPublished in መዝናኛ

 

ግመል በተለይም እንደ አፋር ባሉ በርሃማ አካባቢዎች ላይ ለመጓጓዣነት ብሎም ወተትና ስጋን በመስጠት የምትታወቅ ከመሆኗም በላይ ለአካባቢው ነዋሪዎች የሀብት መለኪያ ብሎም የልብ ወዳጃቸውን መጋበዣም ናት።

በተለይም በአፋር ሞቃታማ ስፍራ በዳሎል ላይ የሚመረተውን ጨው በጀርባዋ ተሸክማና ብዙ ርቀትን ተጉዛ ለገበያ በማቀረብም ለአገሬው ህዝብ የጀርባ አጥነት በመሆን እያገለገለች የምትገኝ እንስሳ ናት። በዚህ ሂደትም በርካታ ግመሎች በመሪዎቻቸው በመታገዝ ሰንሰለታዊ አካሄድን በመከተል ነው አገለግሎታቸውን የሚሰጡት። ይህ ጉዞ ደግሞ በአካባቢው አጠራር «ቅፍለት» በመባል ይታወቃል።

ይህንን የግመሎች ሰንሰለታዊ ጉዞ ወይም ቅፍለትን የተመለከተ ፌስቫል ሰሞኑን ለመጀመሪያ ጊዜ በአፋር ክልል በርሃሌ ወረዳ ዳሎል አካባቢ ተከናውኗል። ፌስቲቫሉ በበርካታ ግመሎች እንዲደምቅ ተደርጓል።

ይህ በዓይነቱ ለየት ያለ ፌስቲቫል በኒም ፕሮሞሽንና በአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን፣ የተለያዩ ዓላማዎችን ማንገቡንም የፕሮግራሙ አዘጋጆች ይናገራሉ።

የፌስቲቫሉ አዘጋጅ ወይዘሪት ኒም ሀጎስ እንደሚሉት ፣ ይህንን የግመል ቅፍለት ፌስቲቫል በየዓመቱ በማዘጋጀት ክልሉን የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ ዋና ዓላማ እንዲሆን ተደርጓል። በሌላ በኩልም የግመል ቆዳ እስከ አሁን ጥቅም ላይ አለመዋሉ ጠቅሰው፣ቆዳ ጥቅም ላይ እንዲውል በተለይም ተመራማሪዎች ግመልን መሰረት ያደረጉ ጥናቶች እንዲያካሂዱ ፌስቲቫሉ በር ከፋች መሆኑንም አብራርተዋል።

«ምንም እንኳን በክልሉ ግመል የተለያዩ ለሰው ልጆች አስቸጋሪ የሆኑ ተግባራትን በመፈጸም ከፍ ያለ ጥቅምን ቢሰጥም ተገቢውን ትኩረት ግን እያገኘ አይደለም፤ በመሆኑም በዚህ ፌስቲቫል አማካይነት ለግመሎች ምስጋና መስጠትም አስፈላጊ ነው» ሲሉ ወይዘሪት ኒም ተናግረዋል፡፤

የፌስቲቫሉ ተሳታፊ አቶ ኡመር ኢብራሂም እንደሚሉትም፤ ግመል የአፋር ክልል ትልቅ ተፈጥሯዊ ሀብት ናት። ይህንን ሀብት ወደ ቱሪዝም መስህብነት ቀይሮ ለመጠቀም እንደዚህ ዓይነት ፌስቲቫሎች አስፈላጊ ናቸው።

ግመል በክልሉ ከምትሰጠው የጭነት አገልግሎት በተጨማሪ ወተቷና ስጋዋም የክብር ምግብና መጠጥ ነው፤ ፌስቲቫሉም የክልሉ ማህበረሰብና ግመሎች ያላቸው ቁርኝት የሚታይበት ይሆናል እንደ አቶ ኡመር ገለጻ።

 

በሪሁ ብርሃኔ

 

 

Published in መዝናኛ

 

ምግቦች እና መጠጦች በተለያዩ ምክንያቶች ሊበላሹ የሚችሉ ሲሆን፣ የአገልግሎት ዘመን ማለፍ እና በአግባቡ ያለመያዝ ለብልሽት ሊዳርጉት ይችላሉ። የተበላሹ ምግቦችና መጠጦች የሰው ልጆችን ጤና ከማወክ አልፈው ለህልፈት ሊዳርጉ ይችላሉ።

በአገራችን በተለይም በመዲናችን በተለያዩ ጊዜያት በአቋራጭ ለመክበር የሚያስቡ ስግብግብ ነጋዴዎች የተበላሹ ምግቦች እና መጠጦችን ለደንበኞች በማቅረብ እንዲሁም በምግብ ላይ ባዕድ ነገሮችን ቀላቅለው ከመሸጣቸው ጋር ተያይዞ ለጆሮ የሚሰቀጥጡ ወሬዎችን መስማት የተለመደ ሆኗል።

ለአብነትም እንጀራ ውስጥ ሰጋቱራ እና ጀሶ ፣ በርበሬ ውስጥ ቀይ አፈር፣ ጠጅ ውስጥ ሲሚንቶ፣ የለውዝ ቅቤ ውስጥ የቀለጡ ባዕድ ነገሮች ተገኘ የሚሉ ወሬዎችን በብዙሃን መገናኛዎች ማደመጥ ተለምዷል ።

በመዲናዋ የህብረተሰቡን ጤና የሚያውኩ ምግቦችን እና መጠጦችን የመቆጣጠር ተግባር የሚያከናውነው የአዲስ አበባ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን 2009 .ም የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ላይ ሰሞኑን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመከረበት ወቅትም ይህ አሳሳቢ ችግር ተነስቷል፡፡

በመድረኩ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ተወካይ አቶ ጸጋዬ ጸድቅ እንደሚናገሩት፤ የህብረተሰቡን ጤና የሚጎዱ ምግብ እና መጠጥ በሚያቀርቡት ላይ የሚወሰደው እርምጃ በቂ አይደለም። በዚህም ምክንያት ነጋዴዎች በየሱፐር ማርኬት የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምግቦችን እና መጠጦችን የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው እንዳልሆኑ አስመስለው እስከ መለጠፍ ደረጃ እየደረሱ ናቸው።

«ይህንን ችግር ለመቆጣጠር እና የባለስልጣኑን አቅም ለማጠናከር ከወንጀል ህጉ በተጨማሪ መሰል የህግ ጥሰት በሚፈጽሙት ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችሉ መመሪያዎች ሊኖሩ ይገባል» ይላሉ።

አቶ አየለ ሰዴ የአዲስ አበባ የልኳንዳ ነጋዴዎች ማህበር ሰብሳቢ ናቸው። «የህገ ወጥ እርድ ስጋ በየ ሱፐር ማርኬት፣ በየምግብ ቤቶች እና ሉካንዳ ቤቶች መሸጥ የተለመደ እየሆነ መጥቷል» ይላሉ። ይህ በመዲናዋ የሚሸጥ የህገ ወጥ እርድ ስጋ ግብር ላለመክፈል በሚል በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ታርዶ ወደ መዲናዋ የሚገባ መሆኑን ይገልጻሉ ።

የአዲስ አበባ ቄራዎች ብቻ ቁጥጥር በማድረግ የህገ ወጥ እርድ ስጋ መከላከል እንደማይቻል በመግለጽ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ከተሞች ላይም ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ ።

ሌላኛው የውይይት መድረኩ ተሳታፊ አቶ ተስፋዬ ገብረ ዮሐንስ ጨው አዮዲን ሳይጨመርበት ጥቅም ላይ እንዳይውል ጥረት ቢደረግም በገበያው አዮዲን ያልተጨመረበት ጨው በስፋት እየተሸጠ መሆኑን ይጠቁማሉ ፡፡ ይህም የሸማቾችን ጤና የሚጎዳ መሆኑን ነው የሚናገሩት ።

እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ፤ የዚህ ችግር ዋናው ምክንያት በከተማዋ ደረጃ ጥብቅ ቁጥጥር ቢደረግም በክፍለ ከተሞች እና በወረዳዎች ደረጃ የሚደረጉ ቁጥጥሮች በጣም ልል ናቸው። የመጠጥ እና ምግብ ድርጅቶችን በመፈተሽ ዕድሳት የሚያደርጉ የባለስልጣኑ ባለሙያዎች ከነጋዴዎች ጋር እንደሚደራደሩም ይገልጻሉ።

የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ እንደተናገሩት፤በከተማዋ አብዛኞቹ ነጋዴዎች እና ባለሃብቶች የህብረተሰቡን ጥቅም የሚጎዱ ምግብ እና መጠጦችን በማስወገድ የተሻለ ተግባር ያከናወኑ ሲሆን፣ ጥቂት ነጋዴዎች በራስ ወዳድነት ችግር እየፈጠሩ ናቸው ፡፡ እነዚህን ድርጅቶች አደብ ለማስያዝ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የአቅሙን እየሰራ ነው ።

በግማሽ ዓመቱ በከተማዋ በሚገኙ የምግብና መጠጥ ድርጅቶች ላይ ቁጥጥር በማድረግ ችግር ያለባቸው አብዛኞቹ አሰራራቸውን እንዲያሻሽሉ የተደረገ ሲሆን ፣ ችግራቸውን መፍታት ባልቻሉ እና የከፋ ችግር በተገኘባቸው 1 466 ተቋማት ላይ ከጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ማሸግ የሚደርስ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ። በተበላሹ ምግቦች ላይም እንዲሁ እርምጃ ተወስዷል፡፡

ከዚህም ጎን ለጎን የህብረተሰቡን ጤና በከፍተኛ ደረጃ ሊጎዱ የሚችሉ 90 ሺ ኪሎ ግራም የተበላሹ ምግቦችን እና ከ30 ሺ ሊትር በላይ መጠጦች እንዲወገዱ ተደርጓል ፡፡

ምክትል ዳይሬክተሯ እንዳሉት ፤ ባለስልጣኑ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው፣ አገልግሎት የማይሰጡና ህገወጥ ምግቦች፣ መጠጦችና የኢንዱስትሪ ውጤቶች አወጋገድ ላይ ጥሩ አፈጻጸም ለነበራቸው 332 ተቋማት ማረጋገጫ በመስጠት የማበረታታት ተግባር አከናውኗል።

71 የውሃ ናሙናዎችን ወደ ላቦራቶሪ በመላክ በማስመርመር ጤንነቱን ለማረጋገጥ ታቅዶ 46 ተልኮ የተመረመረ ሲሆን፣ ከተመረመረው ውስጥ 7ቱ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ መሆኑን በማረጋገጥ የማስወገድ እርምጃ ተወስዷል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ካለው አቅም አንጻር በከተማዋ የሚገኙ የምግብ እና መጠጥ ቤቶችን በመቆጣጠር ብቻ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያደርገው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት አስገኝቷል የሚል ግምት እንደሌላቸውም ነው ምክትል ዳይሬክተሯ ያስታወቁት ። « ችግሩ ሊፈት የሚችለው ሁሉም የተቋማቱ አመራሮች እና ባለሙያዎች በኃላፊነት አገልግሎት ሲሰጡ መሆኑንም አስገንዝበዋል ።

በምግብና በመጠጥ ዘርፍ የተደራጁ የሆቴሎች ማህበራት፣ የነጋዴዎች ፎረሞች በዚህ ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ለባለስልጣኑ በመጠቆም እና በሌሎች እገዛ በማድረግ ለባለሥ ልጣን መሥሪያ ቤቱ የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ይላሉ።

እንደ ምክትል ዳይሬክተሯ ማብራሪያ ፤የተበላሹ ምግቦች እና መጠጦች በተያዙበት ወቅት በአስቸኳይ እንዲወገዱ የሚደረግ ሲሆን በአከፋፋዮች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከፌዴራል አከፋፋዮች ጋር ባለስልጣኑ በጋራ እየሰራ ነው ፡፡

የተወገዱ ምግቦች እና መጠጦች ብዙ ቢሆኑም አሁንም የሚቀሩ ተግባራት መኖራቸውን እና የነጋዴውን አስተሳሰብ ለመቀየር የሚደረጉ ጥረቶች መጠናከር ያለባቸው ናቸው። ባለስልጣኑ የሚያ ደርገው ቁጥጥር እንደተጠበቀ ሆኖ ነጋዴው በራሱ ፈቃደኝነት መወገድ ያለባቸውን እያስወገደ እንዲሄድ ማድረግ ቁልፍ ሥራ ነው።

ህብረተሰቡም ምግብ እና መጠጦችን በሚገዛበት ወቅት የአገልግሎት ጊዜው ያለፈበት መሆን ያለመሆኑን አይቶ መግዛት ይኖርበታል ። በህብረተሰቡ ዘንድ በቀጣይ በዚህ ረገድ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል ።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የአቃቂ ቃሊቲ ከፍለ ከተማ ተወካይ አቶ ጸጋዬ ጻድቅ የተበላሹ እና ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምግቦች እና መጠጦች በሚያቀርቡት ላይ የሚወሰደው እርምጃ አስተማሪ አይደለም የሚል እምነት አላቸው።

በመሆኑም ለሰው ልጆች ኑሮ ወሳኝ በሆኑ ምግቦች እና መጠጦች ላይ በዕድ ነገር ጨምረው የሚሸጡ፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው የፋብሪካ መጠጦችን እና ምግቦችን ለህብረተሰቡ የሚሸጡ ነጋዴዎችና ባለሃብቶች እየተበራከቱ መሆናቸውን ይጠቁማሉ ።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ወረቲ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተሰጡ ኃላፊነቶች በርካታና በባህሪያቸው ውስብስብና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ዝንባሌዎች የሚታይባቸው በመሆኑ የባለድርሻና የህዝብ አደረጃጀቶች ተሳትፎ ወሳኝ ሚና አለው ይላሉ።

በዚህ መሰረት በተፈጠሩ መድረኮች ህብረ ተሰቡን የችግሩ ቁጥጥር ባለቤት ለማድረግ በታለመው መሰረት ህብረተሰቡ ችግሮችን የመጠቆም ልምድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ይህም ወደ ፊት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ለሚደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።

 

መላኩ ኤሮሴPublished in ማህበራዊ

 

የአፍሪካ ህብረት 28ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጥር 22 እና 232009 .ም በአዲስ አበባ አካሂዷል። ህብረቱ በዓመት ሁለቴ ነው መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ የሚያ ካሂደው፤ አንደኛው፤ ሁሌም የህብረቱ ዋና ጽህፈት ቤት በሚገኝበት አዲስ አበባ፤ ሌላኛው የዓመቱ የህብረቱ ሊቀመንበር በሚመራው አገር ይካሄዳል።

የዘንድሮው 2ኛ ጉባኤ የህብረቱ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት አልፋ ኮንዴ በፕሬዚዳንትነት በሚመሯት ጊኒ ይካሄዳል። እናም የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ በራሱ እንግዳ ነገር አይደለም። ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በቋሚነት ሲካሄድ የኖረና የተለመደ ነውና።

የዘንድሮውን የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ልዩ የሚያደርገው ከወራት በፊት በኤርትራ መንግስት ማስታወቂያ ሚኒስቴር አቅጣጫ እየተሰጣቸው የሚሰሩ የማህበራዊ ሚዲያ ድረ ገጾች የነዙት ወሬ ነው። ይህም በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ እንዲታወጅ ያስገደደ የጸጥታ ችግር ስላለ 28ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች መደበኛ ስብሰባ ችግር ይገጥመዋል በሚል የተነዛ ነው።

እነዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ይህን ወሬ ያገኘነው በወቅቱ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ከነበሩት ዶ/ር ኒኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ነው ነበር ያሉት፤ ሆኖም የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ይህን ማለታቸውን የሚያረጋግጥ አንዳችም ማስረጃ አልተገኘም። በመሆኑም ወሬው የፈጠራ ነበር። ወሬው በተነዛበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን እንደቁም ነገር ቆጥሮ ምላሽ አለመስጠቱም ተራ የፈጠራ ወሬ እንደነበረ ያመለክታል።

ያም ሆነ ይህ፤ 28ኛው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ የመሪዎች ስብሰባ ፍጹም ሰላማዊና ስኬታማ ሆኖ ተጠናቅቋል። ጉባኤው አርባ ገደማ የአፍሪካ አገራት መሪዎች፣ የሌሎች አህጉራትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎች፣ በቪአይፒ ሳሎን ያለፉትን ሳይጨምር ከ3 መቶ በላይ የተለያዩ አገራት እና ሚዲያ ተቋማት ጋዜጠኞች፣ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞችና ሌሎች እንግዶች፤ በድምሩ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፈውበታል። እርግጥ፤ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጉባኤው በዚህ አኳኋን እንደሚካሄድ አስቀድሞም እምነት ነበራቸው። መደበኛ ጉባኤው እንዳይካሄድ የማድረግ ከንቱ ህልም የነበራቸው የኤርትራ መንግስትና የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ነን በሚል ሽፋን የሚንቀሳቀሱ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚዎች ብቻ ናቸው።

የጉባኤውን ሰላማዊነት አስመልክቶ በተሳታፊዎች ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል አንድ ሁለቱን ልጥቀስ። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ልዩ አማካሪ ማገድ አብድላዚዝ፣ በአገሪቱና በአዲስ አበባ ያለውን ሰላም አስመልክተው በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ ሃገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ያለች አትመስልም፤ ምንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምልክት የለም። ስብሰባውም በሰላም ተጠናቅቋል። ሰላምን የሚያደፈርስ ምንም አይነት ችግር አላየሁም፡፡› ብለዋል።_ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች መዘዋወራቸውንና ምንም አይነት የጸጥታ ችግር እንዳላጋጠማቸው፣ ሌሎች የጉባኤው ተሳታፊዎችም ወደፈለጉበት ቦታ ያለምንም ገደብና ቁጥጥር በመንቀሳቀስ አገልግሎት ሲያገኙ እንደነበረ መመልከታቸውንም ተናግረዋል። በተመሳሳይ በአፍሪካ ህብረት የኢንዱስትሪ ክፍል ኃላፊ ሃሰን ሁሴን በሰጡት አስተያየት፤ በኢትዮጵያ ሰላም አለ፤ በአገሪቱ ያለው ሁኔታም መልካም ነው፤ ብለዋል። ይህም አገሪቱ ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ ረገድ በትክክለኛ ጎዳና ላይ መሆኗን አመላካች መሆኑንም ገልጸዋል።

በአገሪቱ ጠላቶችና በጉዳይ አስፈፃሚዎቻቸው የተሞከረው ጉባኤውን የማክሸፍ ህልም በዚህ አኳኋን ቅዠት ሆኖ መቅረቱ አንድ ጉባኤውን በልዩነት እንድናስታውስ የሚያደርገን ጉዳይ ነው።

ሌላው በእኔ እይታ 28ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ልዩ የሚያደርገው፤ በአውሮፓና በአሜሪካ ከሚታየው አዝማሚያ የተለየ እውነታ የተንጸባረቀበት መሆኑ ነው። በቅርቡ እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት ራስዋን አውጥታለች። በሌሎችም የአውሮፓ አገራት ተመሳሳይ ዝንባሌዎች እየተንጸባረቁ ነው። አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት መውጣቷን አወድሰውታል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከአገራት ጋር ከመቀራረብ ይልቅ መፋታትን ነው የመረጡት፤ ትራምፕ ፕሬዚዳንት ሆነው በተመረጡ ማግስት አገራቸው ካናዳን፣ አውስትራሊያን፣ ጃፓንን፣ ሜክሶኮን ጨምሮ 12 አገራትን በአባልነት ካቀፈው Trans Pacific Partnership (TPP) አባልነት እንድትወጣ አድርገዋል። ከሰሜን አሜሪካ ነጻ የንግድ ስምምነት (North America Free Trade Agrement _ NATFA) የመውጣት ፍላጎት እንዳላቸውም በምርጫ ፉክክር ዘመቻቸው ሲገልጹ እንደነበረ ይታወሳል።

ታዲያ በዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ በአውሮፓና በአሜሪካ ከሚታየው የመለያያት አዝማሚያ በተቃራኒ ከህብረቱ አባልነት ራሷን አግልላ ለ33 ዓመታት ያህል የቆየችው ሞሮኮ ወደአባልነት ለመመለስ ጥያቄ አቅርባ ህብረቱ ጥያቄውን ተቀብሎ አጽድቋል። የአውሮፓ አገራትና አሜሪካ ወደመለያያት ሲሄዱ አፍሪካውያን ዘንድ ደግሞ ወደመተባባር የመሄድና ህብረትን የማጠናከር አዝማሚያ ታይቷል። ይህ የዘንድሮውን የአፍሪካ ህብረት መደበኛ ጉባኤ ልዩና ታሪካዊ ያደርገዋል።

28ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ባለፉት አራት ዓመታት የህብረቱን ኮሚሽን በሊቀመንበርነት በመሩትና የስራ ዘመናቸውን በጨረሱት ኒኮሳዛና ዴላሚኒ ዙማ ምትክ ቻዳዊውን ሙሳ ፋቂ መሃማት የህብረቱን ኮሚሽን ለቀጣይ አራት አመታት በሊቀመንበርነት እንዲመሩ መርጧል። ጋናዊው ክዌሲ ቋርቴይ ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተሰይመዋል።

የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት የ56 አመቱ ሙሳ መሃማት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2003 እስከ 2005 .ም የቻድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል። ከ2007 እስከ 2008 ባለው ጊዜም የአገሪቱ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው ሰርተዋል። በተመሳሳይ ወቅት የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነውም አገልግለዋል።

28ኛው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ ጉባኤ በርካታ አህጉራዊ ውሳኔዎች የተላለፉበትም ነበር። ህብረቱ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች ዋና ዋናዎቹ መካከል፤ በአህጉሪቱ የገበያ ትስስርን ለመፍጠርና በ2020 ከግጭት የፀዳች አፍሪካን ማየት የሚለው ቀዳሚው ነው። በሊቢያ፤ በሶማሊያ እና በደቡብ ሱዳን የሚታየውን የሰላምና የፀጥታ ችግር ለመፍታት የሚያስችል አቅጣጫም አስቀምጧል። በአፍሪካ አንድ የጋራ ገበያ ለመፍጠር አባል አገራቱ መግባባት ላይ ደርሰዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የ2030 የዘላቂ ልማት ግቦችና የአፍሪካ የ2063 የሰላምና የብልፅግና ግብ ተቀናጅተው እንዲተገበሩ ማድረግ በሚያስችል አጀንዳ ላይም ስምምነት ተደርሳል። ህብረቱን በፋይናንስ ለመደገፍም አባል ካልሆኑ አገራት ወደአባል አገራት በሚገቡ ምርቶች ላይ የዜሮ ነጥብ 2 በመቶ ቀረጥ የመጣል ስምምነትም ላይ ተደርሷል። በእነዚህ ውስጥ የሴቶችንና የወጣቶችን ተጠቃሚነትና ከዚህም ጋር ተያይዞ አጠቃላይ የአህጉሪቱን ህዝቦች ኑሮ ማሻሻል የሚያስችሉ ጉዳዮች ተነስተው ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ፤ የአፍሪካ የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት የ2016 ሪፖርት ቀርቦ የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል። በዚህም በ2016 የሰላምና ፀጥታ ችግር አለባቸው ያላቸውን አገራትና የሚወሰዱ የመፍትሄ ሃሳቦችንም ይፋ አድርጓል። ምክር ቤቱ ጋምቢያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ማሊ፣ ሊቢያ፣ ብሩንዲ፣ ጊኒ ቢሳው እና ምዕራባዊ ሰሃራ የሰላምና ፀጥታ ችግር ያለባቸው በሚል ለይቷል። በጋምቢያ ተካሂዶ በነበረው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የአዳማ ባሮውን ማሸነፍ ተከትሎ ተፈጥሮ የነበረው ችግር፣ በምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) እና በህብረቱ ጥረት መፈታቱንም አንስቷል።

የአፍሪካ የሰላምና የጸጥታ ምክር ቤት የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎችም በ2015 የገቡትን ቃል እንዲተገብሩ ጥሪውን አቅርቧል። በደቡብ ሱዳን ወደ ብሄር ያመራውን ግጭት ለመፍታትም ሁሉንም ወገኖች ያሳተፈ ውይይት እንዲካሄድ አቅጣጫ አመላክቷል። መንግስትም የአፍሪካ ቀጣና የሰላም ጥበቃ ሃይል ወደ ስፍራው እንዲገባ እንዲፈቅድና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በጋራ እንዲሰራ ጠይቋል። አገራትና መንግስታት ችግሩን ለመፍታት የገንዘብ ድጋፍ ያደርጉ ዘንድም ጥሪውን አቅርቧል።

በሶማሊያ በህብረቱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ (አሚሶም) ወታደሮች ክፍያ መቀነስ ጋር ተያይዞ ለተከሰተው ችግር አባል ሃገራቱ ድጋፍ እንዲያደርጉ የህብረቱ የጸጥታ ምክር ቤት ጠይቋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትም ለህብረቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል። በመጨረሻም በ2020 .ም ከግጭት የጸዳች አፍሪካን ለመገንባት አገራት ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል ሲል አሳስቧል። ለዚህም የግጭት መንስኤ የሆኑትን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና ጅኦ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን መፍታትና የባህር ላይ ዝርፊያንና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን መግታት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥቷል።

የአፍሪካ ህብረትና የህብረቱ የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት ያሳለፏቸው ውሳኔዎች በሙሉ ኢትዮጵያ ከምትከተለው የልማትና የሰላም ስትራቴጂ ጋር የተጣጣሙ ናቸው። ህብረቱ የ2063 የሰላምና የብልጽግና ግቡ አካል እንዲሆን የወሰነው የተባበሩተ መንግስታት ዘላቂ የልማት እቅድ የኢትዮጵያ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አካል ሆኖ በመተግበር ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ አህጉሪቱን በንግድ የማስተሳሰሩን እቅድ በተለይ እስከ ሰሜን አፍሪካ በሚዘልቅ የቀጣናው የሃይል ትስስር እቅድ ነድፋ ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች። ላለፉት ሃያ ዓመታትም ለአህጉሪቱ በተለይ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት ልዩ ትኩረት ሰጥታ በግንባር ቀደምትነት እየተንቀሳቀሰች መሆኗም ይታወቃል። ይህ ኢትዮጵያ ህብረቱን እንድትደገፍ ህብረቱም የኢትዮጵያን እቅድ አፈጻጸም እንዲደግፍ የሚያደርግ ሁኔታን በመፍጠር ተግባራዊነቱን ያረጋግጣል።

በአጠቃላይ ሰሞኑን በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ አፍሪካውያን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ግልጽነት ለሰላምና ለብልጽግናቸው በህብረት እንዲቆሙና ህብረታቸውን እንዲያጠናክሩ ማድረግ የሚያስችል ውሳኔ የተላለፈበት ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ፤ በአሜሪካና በአውሮፓ ከሚታየው መለያየትና አንዱ በሌላው ላይ በሩን ከመዝጋት የኋሊት አካሄድ በተለየ ህብረትን የማጠናከር አዝማሚያ የታየበት ነው። ይህም የአፍሪካን የህዳሴ ዘመን መጀመር ያበስራል።

ጽሑፉ የፀሐፊውን አመለካከት ብቻ

የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን።. ነጋሽ

Published in ፖለቲካ

 

ለአገሪቱም ሆነ ለስርዓቱ አደጋ ናቸው ተብለው ከተለዩት አንኳር ጉዳዮች መካከል የመልካም አስተዳደር ችግር ይጠቀሳል፡፡ ችግሩን ለመፍታትም መንግስት በየጊዜው የተለያዩ የማስተካከያ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምና የመልካም አስተዳደር የንቅናቄ ማቀጣጠያ ዕቅድ አውጥቶ በተመረጡ የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቋማት ላይ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ክትትልና ቁጥጥር አካሂዶ ነበር፡፡

የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ሪፖርቱን ይፋ ካደረገ በኋላ የተገኙ ግብአቶችን መሰረት በማድረግ እንዲሻሻሉ ሲል አሳስቦ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ ከዚህ ባሻገርም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ከመልካም አስተዳደር አኳያ የተከናወኑ ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮች እንዲሁም ሳይፈቱ የቀሩ ጉዳዮችን የሚፈትሽና ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ የውይይት መድረክም በአገር አቀፍ ደረጃ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም መልካም አስተዳደርን በአገር አቀፍ ደረጃ ማስፈን አልተቻለም፡፡ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ዜጎች ሮሮ ሲያሰሙ ምሬታቸውንም ሲገልጹ ይደመጣል። በሀገሪቱ ካለፈው አመት አንስቶ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የተቀሰቀሱ ሁከቶችም አንድም የመልካም አስተዳደር ችግር ያስከተላቸው መሆናቸው ይታወቃል፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት መንግስት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ብቻውንም የመልካም አስተዳደር ችግርን መፍታት ይችላል ተብሎ ግን አይታሰብም። የህዝቡ ሚና ወሳኝ ይሆናል ፡፡ የተለያዩ አገራት ተሞክሮም የሚያሳየው ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት በየደረጃው የሚገኙ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች እና የብዙሃን ማህበራት የሚጨወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነው።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች የሚቋቋሙበት ዋና ዓላማ ተወካዮቹ ህዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለአስፈጻሚው አካል እንዲያቀርቡ ለማድረግ ነው፡፡ የምክር ቤቱ አባላትም አስፈጻሚው የሚያከና ውናቸውን ተግባራትን ለህዝቡ ያሳውቃሉ ተብሎም ይገመታል። በመሆኑም መርጦ የላከው ህብረተሰብ ወኪሎቹ የመልካም አስተዳደር ችግርን እንዲፈቱለት ይጠብቃል።

በተመሳሳይ መልኩ ማህበራትም ሲቋቋሙ ዋና ዓላማ አድርገው የሚያስቀድሙት ጉዳይ የአባላቱን መብት ማስጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝም ህብረተሰቡ ከመንግስት ሊያገኛቸው የሚገቡ ጥቅሞች በቅልጥፍና እንዲሁም በሚፈልጉት መጠን እና ጥራት እንዲያገኙ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሰሞኑን የኦሮሚያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ከጨፌ ኦሮሚያ አባላት እና ከብዙሃን ማህበራት የተወጣጡ አመራሮች በተገኙበት በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ያተኮረ ውይይት በቢሾፍቱ ከተማ አድርገዋል፡፡ ውይይቱ ትኩረት አድርጎ የመከረው ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት አባላቱ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ለማስቻል ነው፡፡

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ «የጨፌ አባላት እንዲሁም ብዙሃን ማህበራት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ረገድ ህዝቡ የጣለባቸውን ሃላፊነት የሚጠበቅባቸውን ያህል ተወጥተዋል የሚል ግምት የለኝም» ሲሉ ይገልጻሉ።

እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ የጨፌው አባላት የአስፈጻሚውን አካል የሥራ እንቅስቃሴ በመከ ታተልና በመቆጣጠር ችግር ያለባቸው ፕሮጀክቶች፣ አሰራሮች፣ መመሪያዎች እንዲስ ተካከሉ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ህዝቡን የሚያማርሩ ችግሮችን በመታገልም መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በተመሳሳይ የብዙሃን ማህበራትም የአባላቱን ጥቅም በማስከበር፣ ከመንግስት የሚያገኙትን ጥቅሞች በቅልጥፍና፣ በሚፈለገው መጠን እና ጥራት እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ውስንነቶች እንዳለባ ቸውም ይናገራሉ።

የአባሎቻቸውን መብት እና ጥቅም ለማስጠበቅ፣ የማህበራቱን አደረጃጀት እና አሰራር ለመቀየር፤ እንዲሁም የውስጥ ዴሞክራሲያቸውን ለማጎልበት፣ አቅማቸውን ለማጠናከር እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ጥያቄን ለመፍታት በሚደረገው ሂደት ድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ይላሉ።

እንደ ቢሮው ሃላፊ ማብራሪያ፤ መድረኩ የምክር ቤት አባላት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ያስችላል፡፡ የብዙሃን ማህበራትም ህዝቡን እያሰቃዩ ያሉ ችግሮች እንዲቀረፉ በሚደረገው ርብርብ የጎላ ሚና በመጫወት የተቋቋሙለትን ዓላማ እንዲያሳኩ እና የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ያደርጋል፡፡

እንደ ክልል መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያስችሉ ተግባራትን በቀጣይነት ለማከናወን ታቅዷል፡፡ ምክር ቤቶች፣ የብዙሃን ማህበራት እንዲሁም ሌሎች የህዝብ አደረጃጀቶች ከአስፈጻሚው አካል ጋር የሚገናኙበት፣ የሚደጋገፉበት እና መረጃ የሚለዋወጡበት እንዲሁም የማስተካከያ እርምጃዎች በጋራ የሚወስዱበት የመልካም አስተዳደር ፎረም ለማዘጋጀትም እቅድ መያዙንም ይናገራሉ።

በክልሉ የሚገኙ ሁሉም መስሪያ ቤቶች የመጠን እና የስፋት ልዩነት ቢኖርም የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይስተዋልባቸዋል፡፡ ዘርፎቹን የሚያስተባብሩ አመራሮች በፎረሙ የሚሳተፉበት እድል እንደሚፈ ጠርላቸው በመጠቆም፤ ፎረሙ አንዱ ከሌላው የሚማርበትን እድል ይፈጥራል የሚል እምነትም አላቸው ዶክተር ቢቂላ።

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት ወይዘሮ ዓለምነሽ አስፋው የጨፌ ኦሮሚያ አባል እና የጨፌው የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት በአሁኑ ወቅት የክልሉም ሆነ የአገሪቱ ህዝብ ጥያቄ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው። የመልካም አስተዳደርን ለማስፈን በሚደረገው ሂደት ተመሳሳይ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸው የጨፌ አባላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ በማድረግ ችግሮች ደረጃ በደረጃ እንዲቀንሱ እንደሚያስችል ነው የሚናገሩት።

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የህዝብ ተወካዮች ምን ሚና መጫወት እንዳለባቸው ከመድረኩ ብዙ ትምህርት አግኝቼያለሁ፡፡ በቀጣይ ምን መስራት እንዳለባቸው እስካሁን መስራት እያለባቸው ያልሰሩትን፣ ህዝቡ ምን እየጠየቀ እንዳለ፣ የህዝቡ ጥያቄ በምን አይነት መልኩ መመለስ እንዳለበት እንዲሁም በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ የተካሄዱት ውይይቶች ገንቢ ናቸው ብለዋል ወይዘሮ ዓለምነሽ።

የመልካም አስተዳደር ማስፈኛ መመሪያዎችን ባግባቡ ስራ ላይ ማዋል እና ህዝቡ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ለመልካም አስተዳደር መስፈን የድርሻውን መወጣት አለበት የሚሉት ወይዘሮ ዓለምነሽ፤ በቀጣይም በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ሁሉም የበኩሉን ጥረት ሊያደርግ እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡

«የምክር ቤት አባል እና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንደመሆኔ ለሌሎች አርዓያ በመሆን የመልካም አስተዳደር መመሪያዎችን ማስፈጸም ግዴታዬ ነው»፡፡ የሚሉት የክልሉ የማህበራዊ ዘርፍ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፤ ከዚህ በተጨማሪ ወደ ህዝቡ በመውረድ የሚነሱ ችግሮችን በመለየት ለመንግስት አካል የማቅረብ እና መንግስት የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለህዝብ በማሳወቅ በኩል ድርሻቸውን በመወጣት ህዝቡ የጣለባቸውን ሃላፊነትም እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል፡፡

የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዳይሬክተር እና የአዳማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ፈይሳ አራርሳም፤ የብዙሃን ማህበራት እና የምክር ቤት አባላት የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ የራሳቸውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባቸው ይናገራሉ፡፡ በተደራጀ እና በተቀናጀ መልኩ ከመንግስት ጎን በመሆን የህብረተሰቡን ችግሮች መቅረፍ በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ ትኩረት አድርጎ የተካሄደው ውይይትም ገንቢ እንደነበር ይጠቁማሉ።

የመልካም አስተዳደር ችግር ዓለም አቀፋዊ ይዘት አለው የሚሉት አቶ ፈይሳ፤ በአገሪቱም በተለያዩ መዋቅሮች ችግሩ በስፋት እንደሚስተዋል ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም መንግስት ብቻውን የሚያደርገው ጥረት ውጤት ሊያስገኝ አይችልም ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ባለፉት ጊዜያት በመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት የተቀሰቀሱ የህዝብ ቁጣዎች የአገሪቱ የሰላም እና የደህንነት ችግር እስከ መሆን ደርሰው እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ፈይሳ፤ ችግሩን ፐብሊክ ሰርቫንቱን እና ከደንበኞች ጋር ግንኙነት ያላቸውን በመገምገም ብቻ የሚፈታ አይደለም ሲሉም ይናገራሉ፡፡

ማህበራትም የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ መደረጉ ትልቅ ጥቅም ያስገኛል። ምክንያቱም ማህበራቱ ከህብረተሰቡ የተሰባሰቡ ናቸው፡፡ በመሆኑም የመልካም አስተዳደር ችግሩ ተጎጂ በመሆናቸው ችግሩን መጋፈጥ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የማህበራቱም ግዴታ ነው።

ህብረተሰቡን ያማከለ ንቅናቄ ሁሌም ውጤታማ ይሆናል፡፡ ህዝቡ እና ብዙሃን ማህበራት ነቅተው ከታገሉ ችግሩን ለመቅረፍ ቀላል ነው፡፡ ማህበራት ከዚህ ቀደም የአባላቱን ጥቅም እና መብት ለማስጠበቅ ያደርግ የነበረውን ጥረት በማጠናከር መልካም አስተዳደር ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ውስጥም የሚጫወቱትን ሚና እንዲያጠናክሩ ይደረጋል ሲሉ አቶ ፈይሳ ገልጸዋል።

 

መላኩ ኤሮሴ

Published in ፖለቲካ

ድርጅቱ ከግለሰቦች የሚከራያቸው መጋዘኖች ዋጋ በየጊዜው እየጨመረ ነው፤

 

በንግድ ሚኒስቴር ስር ከተቋቋሙ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ውስጥ የግብርና ምርቶች መጋዘን አገልግሎት ድርጅት አንዱ ነው። ድርጅቱ በ2008.ም ስራውን የጀመረውም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለሚሰበስባቸው ሰብሎች መጋዘን በኪራይ ለማቀረብ ነው።

ድርጅቱ ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የ2009 በጀት አመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የአቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱ እንዳመለከተው፤ የመጋዘን ኪራይ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወደደ በመምጣቱ ተገቢ ላልሆነ ወጪ እየተዳረገ ነው ።

ድርጅቱ አገሪቱ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ያስቀመጠቻቸውን ግቦች ለማሳካት እየሰራ እንደሚገኝ በሪፖርቱ አመልክቶ፣ መጋዘን ከግለሰብ አከራዮች ተከራይቶ ስራውን ማከናወኑ በእቅድ አፈጻጸሙ ብሎም በተቋሙ ትርፋማነት ላይ ከፍተኛ ጫናን እያሳደረ መሆኑን አስገንዝቧል ።

ድርጅቱ የተቋቋመበት ዋና አላማ በግብርና ምርቶች ውስጥ ግብይት ለሚካሄድባቸው ምርቶች የክምችት፣ የጥራት ደረጃና ተጓዳኝ ተግባራትን ማከናወንና የመጋዘን አገልግሎት በተለይም ለቡና፣ለሰሊጥና ነጭ ቦሎቄ መስጠት ነው።

በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ በአገሪቱ 21 ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች ከመክፈቱም በላይ 27 ከመንግስት የተላለፉ መጋዘኖችም አሉት፤ ነገር ግን አገልግሎቱን በእነዚህ መጋዘኖች ብቻ መስጠት የማይቻል በመሆኑ ተጨማሪ 33 መጋዘኖች ከግለሰቦች በመከራየት በአጠቃላይ በ60 መጋዘኖች ውስጥ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ እነዚህን መጋዘኖች በመጠቀምም 347 800 ሜትሪክ ቶን እህል ያከማቻል፡፡

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ምክሩ ደንቢ እንደሚሉት፤ የድርጅቱ መጋዘን አከራይ ደንበኞች በየአካባቢው የሚገኙ ግለሰቦችና ድርጅቶች ናቸው፡፡ ቀደም ሲል በተለይም ከግለሰቦች ይከራያቸው ለነበሩት መጋዘኖች በካሬ ሚትር ከ17 እስከ 18 ብር ይከፈል ነበር ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን እነዚህኑ መጋዘኖች በካሬ ሜትር ከ 60 እስከ 70 ብር ለመከራየት ተገድዷል ፡፡

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ድርጅቱ አገልግሎቱን ሊሰጥ የሚችለው በዚሁ መንገድ ብቻ ስለሆነም በተባለው ዋጋ እየተከራየ እንደሚሰራ ጠቅሰው፣ በተለይ መጋዘን እንደደልብ በማይገ ኝባቸው እንደ ኮምቦልቻ ባሉት አካባቢዎች የመደራደር መብት እንኳን ሳያገኝ አከራዮች በሚቆርጡት ዋጋ እየተከራየ መሆኑን ነው ያመለከቱት። በዚህም ምክንያት ለአላስፈላጊ ወጪ እየተዳረገ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከደንበኞች የሚነሱ ተገቢነት ያላቸው በርካታ ቅሬታዎች መኖራቸውን የሚናገሩት ስራ አስፈጻሚው የቅሬታው መነሻ አገልግሎት አሰጣጡ በተፈለገው ልክ አለመሆኑ እንደሆነ እንረዳለን ይላሉ። ሆኖም በተወሰኑ አገልግሎት መስጫ አካባቢዎች ላይ በዝናብና በመብረቅ ምክንያት የሚዛን አገልግሎት መስጠት አለመቻሉ ከዚህም ጋር ተያይዞ በተወሰነ ደረጃ የደንበኞች መጉላላት እንደተከሰተ ይጠቅሳሉ፡፡

እንደሳቸው ገለፃ፤ እነዚህን ቅሬታዎች ለመፍታትና የተሟላ የመጋዘን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉና አለም አቀፍ ደረጃን ያሟሉ እንደ ምድር ሚዛን፣ናሙና ማውጫ ማማዎች እንዲሁም የደንበኞች ማስተናገጃ ቦታዎችን ያቀፉ የተቋሙ ንብረት የሆኑ መጋዘኖችን መገንባት የግድ አስፈላጊ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡

በእነዚህና በመሳሰሉት ችግሮች ምክንያት ድርጅቱ ያቀደውን መደበኛ ገቢ በታሰው መጠን ማሳካት እንዳልቻለም ዋና ስራ አስፈፃሚው ይጠቁማሉ ፡፡ በ2009 .ም የመጀመሪያ ግማሸ አመት የእቅድ አፈፃጸም ድርጅቱ 20 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ አቅዶ ያተረፈው ግን 14 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑንም በማሳያነት አቅርበዋል ፡፡ይህም የድርጅቱ ትርፍ በ5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ዝቅ እንዳለ ያሳያል፡፡

የድርጅቱ የመጋዘን ኦፕሬሸን ዋና ኦፊሰር አቶ መርጊያ ባይሳ እንደሚገልፁትም ፤ በ2008 .ም ብቻ ድርጅቱደንበኞቹ በመጋዘን ውስጥ ካከማቿቸው ምርቶች 13 ሚሊዮን 297 809 ብር ገቢ ያገኘ ቢሆንም ፣ ከግለሰቦች ለተከራያቸው መጋዘኖች በአመቱ 22 ሚሊዮን 401 707 30 ወጪ አድርጓል ፡፡

አቶ መርጊያ ባይሳ ገቢና ወጪ ላይ ልዩነት ያለው ይህ ልዩነት ‹‹ነን ኦፐሬሽናል›› ከሆኑ ገቢዎች እየተሸፈነ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ድርጅቱ ምርት በሚያጠና ክርበት ወቅት ናሙና ይወስዳል ፡፡ ናሙናው ሶስት ቦታ ይከፈልና አንዱ ደረጃ ሲወጣ ለደንበኛ ይሰጣል፡፡ አንዱ ላቦራቶሪ አናሊስስ ይሰራበታል፣የቀረው ደግሞ ለ20 ቀናት ለሪፈረንስ ይቀመጣል፡፡ ከዚህም እንደሚገኝ ነው የሚናገሩት፡፡ ምርት ገበያ ግብይት ሲያደርግ ከሚያገኘው ኮሚሽን ድርጅቱ እንደሚጋራም ይጠቅሳሉ ፡፡

ስራው አዋጭ እንዳልሆነ ያብራሩት አቶ መርጊያ ከማጠራቀም የሚገኘው የገቢ ዋጋ የተተመነው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት ሲመሰረትም መሆኑን ይናገራል ፡፡ ከዛያ ወዲህ ምንም የተከለሰ ነገር እንደሌለም ያብራራሉ ፡፡ ‹‹ ችግሩን ለይተን አውጥተናል፡፡ በዚህ ሁኔታ እንደ ድርጅት ለመቀጠል አስቸጋሪ ነው፡፡ በራሱ ወጪ ራሱን እየደጎመ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ስለሆነም አጠቃላይ ወጪዎቻችንንና ገቢዎቻችንን ለያይተን በገለልተኛ አካል በማስጠናት ለቦርድ በማቅረብና በማፀደቅ ወደ ተግባር ለመግባት እየተዘጋጀን ነው›› ሲሉም ያስገነዘቡት ፡፡

እንደ አቶ ምክሩ ደንቢ ገለጻ እየተተገበረ ባለው በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መጨረሻ ላይ 11 የሚጠጉ ምርቶችን ወደመጋዘን ድርጅቱ ማስገባት ይጠበቃል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ማሾ እና ቀይ ቦሎቄን ወደ መጋዘን ለማስገባት በሂደት ላይ ነው ፡፡ ይህም ድርጅቱ አሁን ከያዛቸው መጋዘኖች በተጨማሪ መጋዘኖቹን በእጥፍ ማሳደግ ይጠበቅበታል ፡፡

ድርጀቱ በቀጣይ ትርፉን ለማሳደግ እንደ መንግስት ተቋም ከመደበኛ ስራዎች ትርፍ ለማግኘት በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ጭማሪ ለማድረግ (አገልግሎት ክፍያን ከፍ ማድረግ)፣ወጪዎችን ለመቀነስ፣ጎን ለጎንም ሌሎች የቢዝነስ አማራጮችን ለማስፋት መስራት በመፍትሄነት ከተቀመጡት መካከል መሆናቸውን ያብራራሉ።

የመገዘን ደረሰኝ የፋይናንስ አገልግሎት ድርጅቱ በረጅም ጊዜ ያቀደውና ይሄ ድርጅት በአቅም እየጎለበተ ሲሄድ በገበሬ ወይም በአምራቾች ደረጃ ተመርተው ቶሎ ኤክስፖርት የማይደረጉ ምርቶችን / በሃገር ውስጥ ሊሸጡ የሚችሉ ምርቶችን / በመጋዘን ለተወሰኑ ግዜ እንዲቀመጡ በማድረግ የተወሰኑ ኮሚሽን በማስከፈልና ገበሬዎቹ(አምራቾቹ) ገንዘብ ከባንክ የሚገኙበትን ሁኔታ በመፍጠር ለመስራት መታቀዱንም ጠቁመዋል ፡፡

ይህ ሁኔታ ደግሞ ድርጅቱ በአብዛኛው መጋዘኖችን በኪራይ በመጠቀሙ ትርፋማ እንዳይሆን አድርጎታል ይላሉ፡፡ ለዚህም መፍትሄው ድርጅቱ ከኪራይ በመላቀቅ የራሱን ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ መጋዘኖችን መገንባት እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዘውዱ ከበደ ከድርጅቱ ሪፖርት እንደሚሉት፤ ድርጅቱ ከግብይቱ ጋር የሚጣጣም አሰራረር በመዘርጋት ወጪ ቆጣቢ መንገዶችን መጠቀም ይኖርበታል ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም የመጋዘንን ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል ፡፡

 

አስናቀ ጸጋዬPublished in ኢኮኖሚ

የአንጎላ ፕሬዚዳንት ጆሴ ኤድዋርዶ ዶሳንቶስ፤

 

በአሁኑ ወቅት በህይወት ከሚገኙ መሪዎች በአፍሪካ በመሪነት የስልጣን ዘመን የሚደርስባቸው ያልተገኘው የአንጎላ ፕሬዚዳንት ጆሴ ኤድዋርዶ ዶሳንቶስ ለ38 ዓመታት ይዘውት የቆዩትን የመሪነት ቦታ እንደሚለቁ ሰሞኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል። አገራቸው በዚህ ዓመት ክረምት ላይ በምታካሂደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደማይወዳደሩም ባሳለፍነው ዓርብ ፓርቲያቸው ባደረገው ስብሰባ ላይ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።

ይሁንና ኮሚኒዝምን የተካኑ ፣የነዳጅ ዘይት መሐንዲስና አገራቸውን ከፖርቹጋል ነጻ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት በተደረገው የሽምቅ ውጊያም በመካፍል ለአገራቸው ሉዓላዊነት መረጋገጥ ጉልህ አስተዋፆኦ ያበረከቱ አርበኛ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ፕሬዚዳንት ዶስ ሳንቶስ ምንም እንኳን በመሪነት መንበራቸው እንደማይቀጥሉ ቢያስታውቁም ፓርቲያቸውን ግን ከእርሳቸው ሃሳብ በተቃርኖ በመቆም «እርሳቸውም በመሪነት ይቀጥላሉ» የሚል አቋም ይዟል።

ይህን ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች መሰማት የጀመሩ ሲሆን፤እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ፕሬዚዳንቱ የፕሬዚዳንትነት ስልጣናቸውን በማስረከብና ከአገራቸው ይልቅ ፓርቲያቸውን በፕሬዚዳንትነት የሚመሩ ሲሆን፣ በዚህም የፓርላማ አባላት የሚሆኑ ዕጩዎችን በመምረጥ ለመከላከያ እንዲሁም ለፖሊስ ተቋማቱ የሚሆኑ ከፍተኛ ባለስልጣናትን እንደሚሾሙ ነው ያመለከተው፡፡

ከፕሬዚዳንት ስልጣን እንደሚለቁ ይፋ ያድርጉ እንጂ ከዚህ ስልጣናቸው በስተጀርባ አንዳች የመወሰን አቅም እንዲኖራቸው የሚያደርግ ሥራዎችን እየሰሩ ስለመሆናቸው አንዳንድ ምልክቶች ይታያሉ ሲል የተለያዩ የፖለቲካ ምሁራን አስተያየታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።

ተቃዋሚዎቻቸው ግን ፕሬዚዳንቱ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ስልጣናቸውን እንደሚለቁ የገቡትን ቃል በማጠፍ እንደሚታወቁ በመጥቀስ የአሁኑ ውሳኔያቸውን በጥርጣሬ እንደሚመለከቱት እየገለጹ ሲሆን፤ በርካቶችም ይህን የ74 ዓመቱን ፕሬዚዳንት ቀጣይ ዕቅድ እንደ አልሸሹም ዞር አሉ ነው ሲሉ ተሳልቀውበታል።

በአፍሪካ ለረጅም ጊዜ በፕሬዚዳንት ስልጣን ላይ ከቆዩት ከኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዚዳንት ቴድሮ ኦቢያንግ ንጉዌማ ማባሶጎ ቀጥሎ ሁለተኛው መሪ መሆናቸው የሚነገርላቸው ፕሬዚዳንት ዶስ ሳንቶስ፤በስልጣን ዘመናቸው የአንጎላን የነዳጅ ሀብት አለአግባብ በመጠቀም በአብዛኛው ዘመዶቻቸውንና የፖለቲካ አጋሮቻቸውን ተጠቃሚ አድርገዋል በሚል ይታማሉ።አንጎላን በእርሳቸው የፕሬዚዳንትነት ዘመን በዓለም በሙስና የተጨማለቀ አስተዳደር ያለባት ሀገርም እንድትሆን አድርገዋታል ሲሉም በርካቶች ይተቿቸዋል።

አንጎላ በነዳጅ ዘይት ሀብት የበለጸገች እንዲሁም ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገሮች ኢኮኖሚዋ በጠንካራነቱ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም፣መረጃዎች እንደሚጠቁሙት 22 ሚሊዮን የሚሆነው የአገሪቷ ህዝብ የሚኖረው በደህንት አረንቋ ውስጥ ነው።

በርካታ አንጎላውያን ፕሬዚዳንቱን በሀገሪቱ እ..አ በ2002 የበቃውንና ለ27 ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት ተከትሎ ከደረሰባት ውድቀት እንድታገግም ያደረጉ በሚል ትልቅ ክብር ሲሰጧቸው፤አንዳንዶች ደግሞ ሀገሪቱ ከነዳጅ ዘይት የምታገኘውን ሀብት ፍትሀዊ በሆነ መልኩ የማያከፋፍሉ አምባገነን በማለት ይወቅሷቸዋል።

18 ዓመት በዕድሜ ከሚበልጧት ቀድሞ ሞዴል ከነበረችው የአውሮፕላን አስተናጋጇ አና ፓውላ ጋር የትዳር ሕይወታቸውን የሚመሩት ዶስ ሳንቶስ የፕሬዚዳንትነት ስልጣኑን በቤተሰብ በመያዝ ከሕይወት ዘመናቸውም ባሻገር ስልጣን ተቆናጥጦ ለመቆየት ሀሳቡ ነበራቸው በሚል ይተቹ ነበር፡፡ፕሬዚዳንቱ ሴት ልጃቸውን ኢሳቤል ዶስ አንቶስ ሶናንጎል የተሰኘው የሀገሪቱ መንግሥት የነዳጅ ኩባንያ ኃላፊ በማድረግ ባለፈው ዓመት መሾማቸው እንዲሁም ወንድ ልጃቸውን ጆሴ ፊሎምኖን የአንጎላ የውጭ ሀብት ፈንድ ሊቀመንበር አርገው መሾማቸውንም ለዚህ በአብነት ያነሳሉ ፡፡

የኤንኬሲ የአፍሪካ ኢኮኖሚክስ የፖለቲካ ተንታኙ ጌሪ ቫን ሰታዴን ‹‹ እውነተኛ ዜና ሊሆን የሚችለው በእርግጥ ዶስ ሳንቶስ ስልጣናቸውን ያስረክቡ ይሆን የሚለው ነው›› በማለት ጉዳዩን ይገልጸዋል። ተንታኙ ፕሬዚዳንት ዶስ ሳንቶስ ወሳኝ በሆነው የፓርቲው የፖለቲካ ስልጣን ላይ ስልጣን መጨበጣቸው በመቆጣጠሩ ላይ እንደሚቆዩ ያመለክታል ነው ያሉት ፡፡

በሀገሪቱ ለዓመታት ሲካሄድ የቆየው ጦርነት ካበቃ በኋላ የፕሬዚዳንት ዶስ ሳንቶስ ፓርቲ ለሦስት ጊዜ ያህል በተካሄዱ የፕርላማ ምርጫዎች በተከታታይ ማሸነፉ ይታወቃል፡፡ አንጎላ በቀጥታ ፕሬዚዳንት መርጣ የማታውቅ ሲሆን አሸፊው ፓርቲ ግን በፓርላማ በሚካሄድ የድምጽ አሰጣጥ ፕሬዚዳንት ይመረጣል። በዚህ ረገድ ገዢው ፓርቲ ኢምፒልኤ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ አጋጥሞትም አያውቅም። አሁንም ቢሆን ፕሬዚዳንቱ ለምርጫ እንደማይወዳደሩ ቢያስታወቁም ገዥው ፓርቲ የአንጎላ ህዝቦች ነጻ አውጭ ንቅናቄ የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ሎሬንሶ ወደ ፕሬዚዳንታዊ መንበሩ እንደሚመጡ ይጠበቃል፡፡

62 ዓመቱን የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ጆ ሎሬንሶ በምርጫው ለፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ በእጩነት የሚያቀርባቸው መሆኑንም በአንድ ወገን እየተወራ ሲሆን፤የፖለቲካ ምሁራንም ሎሬንሶን በአቋማቸው ግትር እንዳልሆኑ በመጠቆም፤‹‹ሎሬንሶ አንጎላ ለምታደርገው ሽግግር ትክክለኛ ሰው በመሆን እንደ ድልድይ ሊያገልግሉ ይችላሉ ሲሉ እያሞካሿቸው ይገኛሉ።

 

ኃይሉ ሳህለድንግል

 

Published in ዓለም አቀፍ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።