Items filtered by date: Wednesday, 08 February 2017

 

  ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሜልቦርን ኦሊምፒክ ለመሳተፍ አምስት የስፖርት ዓይነቶችን በዓለምአቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ማስመዝገብ ነበረባት። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ የስፖርት አባት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ካስመዘገቧቸው የስፖርት ዓይነቶች አንዱ ቅርጫት ኳስ ነበር። ቅርጫት ኳስ በኢትዮጵያ ረጅም ዓመት ያስቆጠረ ስፖርት ቢሆንም የዕድሜውን ያህል አላደገም። ስፖርቱ በቀላሉ በህዝብ የሚወደድና በትንሽ አቅም መስፋፋት የሚችል ቢሆንም የዓለምአቀፉ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጃቸው ውድድሮች በወንዶች ብሔራዊ ቡድን መስርቶ ከተሳተፈ ግማሽ ምዕተ ዓመት አስቆጥሯል። በሴቶቹም ቢሆን በፊባ አፍሮ ቅርጫት ኳስ ውድድር እኤአ በ2011ተሳታፊ ለመሆን በማጣሪያ ውድድሮች ጥሩ እንቅስቃሴ ቢያሳይም ረጅም ርቀት እንዳልተጓዘ ይታወሳል። ስፖርቱ ከመዋቅር ጀምሮ ያሉ ክፍተቶች ቢኖሩበትም የገንዘብ አቅም ዋነኛ ችግሩ እንደሆነ ይነገራል።

      ቅርጫት ኳስ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ተወዳጅ ስፖርት ነው፤ በተለይም በከተማ አካባቢዎች ወጣቱ ዘወትር በትምህርት ቤቶች የሚያዘወትረው ስፖርት ቢሆንም ተወዳጅነቱን ወደ ገንዘብ የሚቀይር መሪ ባለማግኘቱ ዕድገቱ ላይ ተጽዕኖ አሳድሮበታል። ይህን ስፖርት ለማነቃቃትና እንደሌሎች ስፖርቶች ብሔራዊ ቡድን ለማቋቋም በቅርቡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ቆርጠው መነሳታቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጹ ተደምጠዋል።

       ዶክተር አሸብር በኢትዮጵያ ስፖርት አመራር ውስጥ አዲስ አይደሉም። ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በፕሬዚዳንትነት በመምራት ፊፋና ካፍን ከመሳሰሉት ዓለምአቀፍና አህጉር አቀፍ የእግር ኳስ ተቋማት ጋር ጥሩ ግንኙነትና ተሰሚነት እንደነበራቸው  የስፖርት ቤተሰቡ ያውቃል። ከእዚህ በተጨማሪ የተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆንና በታላላቅ አገራዊ አህጉራዊ ኃላፊነቶች ላይ በመሥራትም ይታወቃሉ። እኚህ የቢዝነስ ሰው በተለያዩ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችም የተዋጣላቸው እንደሆኑ ብዙዎች ይመሰክራሉ። ዶክተር አሸብር ከአዲስ ዘመን ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡበት ቃለ ምልልስ የሚከተለውን ይመስላል።

     አዲስ ዘመን፡- ዶክተር አሸብር የኢትዮጵያን ቅርጫት ኳስ እንዴት አገኙት? ምን ዓይነት ቅርፅ ይዞስ ጠበቀዎት?

     ዶክተር አሸብር፡- የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን እንደነባርነቱና እንደ ስሙ ብዙም በጠበኩት ደረጃ አላገኘሁትም፤ በቢሮ ደረጃ እንኳን  ደህና ቢሮ የለውም፤ ከቆርቆሮ ግርግዳና ጣሪያ በተሠራ ቤት ሁለትና አንድ ሰው ማስቀመጥ የሚችል ነው፤ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ሰባት ሰው እንኳን በአንዴ ሊቀመጥበት የማይችልበት ነው፤ የጽህፈት ቤት ኃላፊው እዚያ ውስጥ በፀሐይ እየተቃጠሉ ነው የሚሠሩት፤ ይህን ስመለከት በጣም የሚያሳዝንና የሚያስደነግጥ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ፌዴሬሽኑ ብሔራዊ ፌዴሬሽን ሆኖ ብሔራዊ ቡድን የለውም፤ ይህ ነባር ለሆነ ፌዴሬሽን አስደንጋጭም ነው። አደረጃጀቱንም ብታየው ጠንከር ብሎ በቋሚ ኮሚቴዎች የተዋቀረ አይደለም። በሙያተኛ ደረጃም ብታየውም የኃላፊውም የቴክኒክ ባለሙያውም እውቀት ቢኖራቸውም የበለጠ ጉልበት እንዲያገኙ የተደረገበት አግባብ የለም፤ በፋይናንስ ደረጃም አካውንቱ ውስጥ አንድ ሳንቲም እንኳን የሌለው ፌዴሬሽን ነው። በትጥቅና በፕሮጀክት ደረጃ በደንብ ያልተያዘ ፈተናችን ነው ብዬ ነው የወሰድኩት።

    አዲስ ዘመን፡- የፌዴሬሽኑ አንድ ችግር የፅሕፈት ቤት ችግር እንደሆነ ገልጸዋል፤ እርስዎም ይህን ችግር ለመቅረፍ በራስዎ ወጪ ቢሮ ተከራይተዋል። አዲሱ ቢሮ የሕንፃ ወይንም ቦታ ቅያሬ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ መዋቅራዊ ለውጦችንም ይዞ ይመጣል ብዬ እገምታለሁ፤ በዚህ ረገድ ይህን መዋቅራዊ ለውጥ እተገብራለሁ ብለው እንደ ምሳሌ የሚያነሱት ነገር ይኖራል?

        ዶክተር አሸብር፡- በዋናነት የአራት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ እያወጣን ነው፤ በዚያ ውስጥ ብዙ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እየሠራን ነው። ከዓለምአቀፉ የቅርጫት ኳስ  ፌዴሬሽን ፌዴሬሽናችንን ለመጎብኘት አንድ ሰው መጥተው ነበር፤ በወቅቱ ደንግጠው የተመለሱበት ሁኔታ ነበር፤ ከዚህ አኳያ ቢያንስ ለጊዜው ቢሮውን ማስተካከል የግድ ነበር፤ ቢሮ መከራየት ነበረብን ተከራይተናል። መዋቅሩ ላይ የግድ መሥራት ስላለብን ቋሚ ኮሚቴዎችን እንደገና ማደራጀቱን ቅድሚያ እንሰጣለን። በዚህም የስፖንሰርሺፕ ኮሚቴ፤ ዓለምአቀፍ ግንኙነት፤ የውድድር አዘጋጅ ኮሚቴ፤ የዳኞች ኮሚቴ፤ የቴክኒክ ኮሚቴ፤ የህክምና ኮሚቴና የመሳሰሉትን በዋናነት እንደገና የማዋቀር ሥራ ተግባራዊ እናደርጋለን። ለዚህም አገሪቱ ላይ አሉ የተባሉ ሙያተኞች፤ ስፖርቱ ይጠቅመናል ብለው የሚያስቡ ሰዎችን (ስፖርቱን መርዳት የሚለውን ቃል መጠቀም አልወድም፤ በዕርዳታ መተዳደር የለብንም፤ ስፖርቱ የራሱ ሀብትና ምርት አለው ሊሸጥ ይችላል ብለው የሚያምኑ ሰዎችን) ማሰባሰብ ምርታችንን ማሳደግ፤ ውድድሮቻችንን ጠንካራና ተመልካች ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ፤ የአገር አቀፍና ዓለምአቀፍ ማህበረሰቦችን በስፖርቱ ዙሪያ ማሰባሰብና የውጭ ግንኙነታችንን ማጠናከር አለብን።

       ወደ አሜሪካ፤ ካናዳና ስፔን የመሳሰሉ አገራት ሲኬድ ስፖርቱ ተወዳጅ ነው፤ እነዚህን አገራት ጨምሮ ከዓለምአቀፍ ፌዴሬሽኑ ጋር ለመሥራት መስመሮችን እያመቻቸን እንገኛለን። ዞሮ ዞሮ ሁሉም ነገር እቅዳችን ውስጥ ተካቶ እንዲሄድ እንፈልጋለን።

       አዲስ ዘመን፡- ወደ ፌዴሬሽኑ ሲመጡ ብሔራዊ ቡድን ሊኖረን ይገባል የሚል አቋም ይዘው ነው፤ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ይሄን እንዴት ተቀበለው?

      ዶክተር አሸብር፡- የሚያስደስተው ነገር የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ብዙዎቹ ተጫውተው ያለፉና ለስፖርቱ የተለየ ፍቅር ያላቸው ናቸው፤ ይሄ ትልቅ ጉልበት ነው ለእኛ፤ ሙሉ ፍላጎትና ጉጉት ስለነበራቸው በደስታ ነው የተቀበሉት፤ ብሔራዊ ቡድኑን ለማቋቋም ቴክኒክ ኮሚቴው የራሱን የማቋቋሚያ መስፈርት እንዲያወጣ አድርገናል፤ አሠልጣኝ መቅጠር ስላለብንም ማስታወቂያዎች እያወጣን ነው፤ በቅርቡ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ብሔራዊ ቡድን ይኖራል፤ ወደ ዓለምአቀፍ ጨዋታዎችም ሆነ የወዳጅነት ጨዋታዎች የሚመለስበትን መንገድ እያመቻቸን ነው። ከምንም በላይ ግን ስፖርቱን በአማተርነት ከሚያገለግሉት ሰዎች ጋር ተባብረን መሥራታችን ጥቅም አለው።

       አዲስ ዘመን፡- ቅርጫት ኳስ በባህሪው በቀላሉ በህዝብ የሚወደድ ስፖርት ነው። ይህ ደግሞ ስፖርቱን ወደ ገንዘብ የሚቀይረው ሰው ከተገኘ በቀላሉ ሀብት ማመንጨት እንዲችል ያደርገዋል። እርስዎ ደግሞ በዚህ የተዋጣልዎ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። በዚህ ረገድ ቅርጫት ኳስ ትክክለኛውን ሰው አግኝቷል ማለት እንችላለን?

     ዶክተር አሸብር፡- እኔ ትክክለኛ ልሁን አልሁን አላውቅም፤ ነገር ግን የተለየ ፍላጎት አለኝ። ስፖርቱን ለማገዝም ነው የመጣሁት፤ እኔ ብቻዬን ሳይሆን ከፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለውጥ እናመጣለን ብለን እናስባለን፤ አሁን በቅርቡ ከምንጀምራቸው ውድድሮች የቺልቼር ቅርጫት ኳስ ጥሩ ጅምር ላይ ነው ያለው፤ በአብዛኛው የትም አገር ሲኬድ ቅርጫት ኳስ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚዘወተር ስፖርት ነው፤ ትንሽ ሜዳ የሚፈልግና ብዙ ወጪ የማያሻው መሆኑ ለወጣቶችም ለትምህርት ቤቶችም ምቹ ነው። ለዚህ ትምህርት ቤቶችን ለይተን በሊግ ደረጃ ውድድሮችን ለማካሄድ ጥናት ጨርሰናል። ትምህርት ቤቶች የራሳቸው የውስጥ ውድድር አላቸው። ከዚህ ወጥተው በዞንና በአገር አቀፍ ደረጃ ብሎም በዓለምአቀፍ በተለይም ከአሜሪካ ትምህርት ቤቶች ጋር የሚወዳደሩበትን መድረክ እያመቻቸን ነው። እነርሱም ትልቅ ፍላጎት አላቸው። ክልሎችም በዚህ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ያላቸውን አቅም ተጠቀመው ጎልተው እንዲወጡ እየዞርን ከተለያዩ ክልሎች ጋር ለመሥራት አስበናል። የመከላከያ፤ ፖሊስና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስፖርትንም ለማካተት አስበናል። በዚህም መንገድ የተሻለ ነገር ላይ እንደርሳለን አቅሙም አለን።

      አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ፊፋና ካፍን ከመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማት ጋር ጥሩ ግንኙነትና ተሰሚነት ነበረዎት። አሁንስ ከቅርጫት ኳስ ተመሳሳይ ዓለምአቀፍ ተቋማት ጋር ያለዎት ግንኙነት ምን ይመስላል?

      ዶክተር አሸብር፡- የዓለም አቀፉ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን እንደ ፊፋ ወደ ታች ወርዶ መሥራቱን ወደ ፊት ነው የማየው። ነገር ግን ከኛ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለው፤ ከአፍሪካውም፤ ከአሜሪካውም ጋር ጥሩ ግንኙነት አለን። በእርግጥ እንደ ፊፋ ወጥ አይደለም። ዓለምአቀፉ ፌዴሬሽን አለ፤ የአሜሪካን ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን አለ፤ ኢንተርናሽናል ፌዴሬሽን ተብሎም አለ፤ የእነዚህ ፌዴሬሽኖች መኖር በየዞኑ ካሉት ጋር ተዳምረው ለእኛ ትልቅ ግብዓትና ጉልበት ይሆኑናል። በዋናነት ግን የራሳችን የውስጥ ጥንካሬ ነው የውጪውን ሊያጎለብትልን የሚችለው። እግር ኳስ ላይ እያለንም ብዙ ሥራዎችን በመርህ ወደ መሬት አውርደን በመሥራታችን ነው የወደዱን። ለግል ጥቅም ወይንም ሁልጊዜ ለዕርዳታ ስለማንሄድ፤ የአገራችንን ክብር ጠብቀን መብታችንን በማይነካ መልኩ ስለሄድን ነው የወደዱን። አሁንም በዚህ መንገድ ይሳካልናል ብለን እናስባለን።

      አዲስ ዘመን፡- እንደ ሌሎች ስፖርቶች ሁሉ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስም ብዙ ችግሮች አሉበት። እናንተ በተለየ መልኩ የቅርጫት ኳስ ችግር ይሄ ነው፤ እዚህ ላይ መሥራት አለብን ብላችሁ ነቅሳችሁ ያወጣችሁት ችግር አለ?

       ዶክተር አሸብር፡- ቁልፍ ችግሮቻችንን እየለየን ነው ያለነው፤ እቅዶቻችን ውስጥም አብሮ የሚገባ ነው። በዋናነት ግን ትልቁ ችግራችን ከታች ከታዳጊዎች ጀምሮ በተጠናከረ ሁኔታ ያልተሠራበት ስፖርት መሆኑ ነው። ይህን ችግር ከፈታን የትኛውንም ችግር ይፈታልናል፤ ከታች ጀምረን ጠንካራ ሊግ መሥራት ከቻልን፤ ጠንካራ ፕሪሚየር ሊግና ብሔራዊ ቡድን መሥራት ከቻልን የገንዘብ ችግራችንን መፍታት እንችላለን። ምክንያቱም ጥሩ ምርት አለን መሸጥ እንችላለን፤ ሁሉንም ወደኛ በመሳብ በምንፈልገው አግባብ እንዲመጣ ማድረግ እንችላለን፤ ብሔራዊ ቡድኑና ክለቦች የተለያዩ ዓለምአቀፍ ውድድሮችን ሲያሸንፉና ሲሳተፉ ገፅታችንን እንገነባለን። ይህን ማድረግ የምንችለውም ከታች ጀምረን መሥራት ስንችል ነው።

     አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያን ቅርጫት ኳስ እዚህ ደረጃ አደርሰዋለሁ ብለው የሚያስቀምጡት ህልምዎ ምንድንነው?

      ዶክተር አሸብር፡- ቢያንስ በእኛ ጊዜ በአፍሪካ ደረጃ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሊሆን ይገባል የሚለው ትልቁ ግባችን ነው። መቶ ሚሊዮን ህዝብ ይዘን አምስትና ስድስት ተጫዋች ስናጣ ለሚሰማውም ከባድ ነው። ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ገንብተን የአገራችንን ገፅታ እንገነባለን የሚል ህልም አለኝ። የብሔራዊ ፌዴሬሽናችንን አቅምም በዚያው እንገነባለን፤ በዞንና በአህጉር ደረጃ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆነን ማየት እፈልጋለሁ። ብሔራዊ ቡድን የአንድ ፌዴሬሽን ጉዳይ አይደለም፤ የአገርና የመንግሥት ጉዳይ ነው። ይሄ ፌዴሬሽን በዓመት የሚያገኘው ከሦስት መቶ ሺ ብር የማይበልጥ ነው፤ ዛሬ አንድ ጉባዔ ስትጠራ እንኳን ይሄ ገንዘብ አይበቃም፤ አገራችን አድጋለች ፤ ስፖርቱም አብሮ የሚታገዝበት ደረጃ ላይ ደርሷል ተብሎ ነው የሚታመነው ፤ የመንግሥት አካላት በተለይም ስፖርት ላይ የተመደቡት አዲስ ስለሆኑ ያለውን ችግር በጋራ እያየን ስፖርቱ ለአገር ጠቃሚ እንዲሆን መሥራት ይኖርብናል።

      አዲስ ዘመን፡- ከወር በኋላ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሂዳል። በዚህ ጉባዔ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሚካሄድም ይጠበቃል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በርካቶች እርስዎ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት እንደሚሆኑ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። በዚህ ላይ  ምን ምላሽ አለዎት?

       ዶክተር አሸብር፡- ቀደም ሲል የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የነበሩት ብርሃነ ኪዳነማርያም የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንትም ጭምር ነበሩ። በዚህ የተነሳ እኔ የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ስሆን በቀጥታ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት የምሆን የሚመስላቸው ስላሉ ነው ይሄ ነገር የሚነሳው። ምርጫው መቼ እንደሚካሄድም አላውቅም፤ በዚህ ጉዳይ ላይ አስቤም ተወያይቼም የማውቅበት አጋጣሚ የለም፤ አሁን ያለሁበት ኃላፊነትም ቀላል አይደለም፤ ቅርጫት ኳስ ላይ ጠንክሬ መሥራት ከቻልኩም ቀላል አይደለም።

      አዲስ ዘመን፡- የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ያላሳካሁት አሁን ቅርጫት ኳስ ላይ አሳካዋለሁ ብለው የሚያነሱት ነጥብ ይኖራል?

      ዶክተር አሸብር፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ የሚያሳዝነኝ ነገር ቢኖር ሁልጊዜ ጭቅጭቅ መኖሩ ነው። ይሄ ድሮም ነበር አሁንም አለ ለምን እንደሆነ ግን አላውቅም። ብዙ ጊዜ ግጭት ፈጣሪዎቹ የተወሰኑ ሰዎች ናቸው፤ የማትፈልገው ጣጣ ውስጥ የሚከቱህ ወቅት ብዙ ነው፤ ስፖርት በጣም ብዙ ተንኮሎች ያሉበት ቦታ መሆኑን ተምሬያለሁ። አሁን ባለሁበት ዕድሜ የአገር ውስጡንም የውጭውንም ስፖርት ባህሪውንም ህጉንም ሌላውንም ነገር ጠንቅቄ አውቃለሁ፤ ከእግር ኳሱ ያገኘሁት ትልቅ ትምህርት ነገሮችን በጣም በትዕግስትና በጥበብ ማየትን ነው። አሁን እግር ኳስ ላይ እንዳለው ዓይነት ጭቅጭቅ ይገጥመኛል ብዬ አላስብም ቢገጥመኝም ያለኝ ተሞክሮ በጥሩ መልኩ እንድመራው ያደርገኛል ብዬ አስባለሁ።

       አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻም ስለ ኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ መነሳት አለበት የሚሉት ሃሳብ ካለ ዕድሉን ሰጥቼ ጥያቄዬን ልቋጭ።

        ዶክተር አሸብር፡- አገራችን በስፖርቱ ዘርፍ በተለይም ከአትሌቲክስ በቀር በብዙዎቹ ውጤት እያመጣች አይደለም፤ ህዝባችንም እርካታ አግኝቷል ብሎ መደምደም አይቻልም፤ ስለዚህ ሁላችንም የስፖርት ቤተሰቦች፤ መንግሥትም አንድ ሆነን ለኢትዮጵያ ስፖርት መቆምና የአገራችንን ህዳሴ በስፖርቱም ዘርፍ ለማስቀጠል በጋራ መነሳት እንዳለብን ጥሪዬን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።

    አዲስ ዘመን፡- ዶክተር አሸብር ጥያቄዎቼን ለመመለስ ፍቃደኛ ሆነው ለሰጡኝ ጊዜ አመሰግናለሁ።

      ዶክተር አሸብር፡- እኔም አመሰግናለሁ።

 

ቦጋለ አበበ

Published in ስፖርት
Wednesday, 08 February 2017 20:07

አያ ጅቦ እንከባበር ...

አያ ጅቦ በከተማችን እግር አብዝቷል፤

  የቄራን  መንገድ  የኋልዮሽ ትቶ ሽቅብ ወደ ሜክሲኮ አደባባይ መገስገስ የጀመረው እንግዳ የከተማው መብራትና የሰዎች ግርግር ያሰጋው አይመስልም። ገልመጥ ገልመጥ እያለ ሩጫውን ቀጥሏል። ማንነቱን አውቀው «እግሬ አውጭኝ» ያሉ የምሽት መንገደኞች ድንጋጤና ጩኸትንም ከምንም አልቆጠረም። የት እንደሚደርስ ባያውቀውም  ፍጥነቱን ግን መግታት አልፈለገም።

     ምሽት ሦስት ሰዓት ከሠላሳ ሆኗል። ቀኑ ቅዳሜ በመሆኑ የማታ ተማሪዎችም ሆኑ ቆየት ብለው ቤታቸው የሚገቡ መንገደኞች ቁጥር ቀንሷል። ሆኖም ሰዓቱ እምብዛም አልገፋምና መንገዱ ጭርታ አይታይበትም። አያ ጅቦ ግን ይህ ሁሉ ለእሱ ምኑም አልነበረም። ውሻ መስሏቸው ያለፉትን እያለፈ፣ ጠርጥረው የተጠጉትን  ሁሉ እየነከሰ ወደፊት መገስገሱን ቀጥሏል።

      ሜክሲኮ አደባባይ ኬኬር ሕንፃ አካባቢ ሲደርስ አያ ጅቦ መሆኑን የለዩ ሰዎች ከኋላው እየተከተሉ ያሯሩጡት ያዙ። የአሁኑ ግብግብ  ግን ከባለመኪናዎች ጋር በመሆኑ እንደእግረኞቹ ተጓዦች ሁሉ  በቀላሉ ሊመክታቸውም ሆነ ቀረብ ብሎ ሊነክሳቸው ዕድሉን አላገኘም። ወዲያውም እዚያው በሚገኘው አፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ አካባቢና ሰወር ወዳለው  የጨለማ ስፍራ ገብቶ እግሬ አውጭኝ ማለቱን ቀጠለ። ወደ ፌዴራል  ፖሊስ ካምፕ እንደተጠጋም ክፍት ሆኖ ባገኘው በር በፍጥነት  ወደ  ውስጥ  በመዝለቅ ድምፁን አጥፍቶ  መሸገ።

    በፋና ብሮድካስቲንግ  ኮርፖሬሽን ለደራው ጨዋታ ዝግጅት ክፍል የምሽቱን እውነታ የጠቆመው የዓይን እማኝ  ወጣት እንደገለጸው ከሆነም፤  በዕለቱ በሥራ ላይ የነበሩ የፖሊስ አባላት ሳይቀሩ በዚሁ ጅብ ተነክሰው ጉዳት ደርሶባቸዋል። እሱ እንዳለውም  የአያ ጅቦ ንክሻ ካረፈባቸው ፖሊሶች አንደኛው በእጁ  ላይ ያጋጠመው ጉዳት የከፋ  ሆኗል። እናም ጣቱ ሊቆረጥ ይችላል የሚል ስጋት ጭምር ተፈጥሯል።

       «ምን ሲደረግ መጣህብን» ባሉ ሰዎችና «መብቴ ነው» የሚል በሚመስለው ጅብ መካከል በነበረው ግብግብ የወጣቱን የቅርብ ጓደኛ ጨምሮ ሌሎች መንገደኞች ጉዳት አጋጥሟቸዋል። ሌላዋ በአካባቢው የነበረች የዓይን እማኝም ኑሮዋ  ደብረወርቅ ሕንፃ ጀርባ ከላስቲክ በተሠራው ቤት ውስጥ እንደመሆኑ ምሽቱን  በሰዎችና በጅቡ መካል የነበረውን ሁኔታም በቅርበት ሆና ተከታትላለች። ዓመታትን በላስቲክ ጎጆዋ፣ በጨለማውና ሰዋራ  ስፍራ የገፋች ቢሆንም የዚያንለታው አጋጣሚ ግን ለእሷ የመጀመሪያዋ ነበር። ደግነቱ ይህን ሁሉ ጉዳት በሰዎች ላይ ያደረሰው ድንገቴ እንግዳ  ጅብ ነውና ይገደል ዘንድ ግድ ሆኗል።

     ወዳጆቼ! የሆነስ ሆነና የጅቦች ከተሜነት ማብዛትንና  የሰዎች  ተደጋጋሚ  ስጋትን  እንደምን ታዩታላችሁ? እንዴ ይሄ ጉዳይ እኮ ከአንድ አይሉት ሁለቴ በተለያዩ ጊዜያት እያጋጣመን ነው። እነዚህ ጫካ ለምኔ ጅቦች የሰው በር እየገፉ፣የለቅሶ ቤት ድንኳን እየሰበሩና ያለሰዓታቸውና ያለቦታቸው እንዳሻቸው በየመንገዱ እየዞሩ  ነው።

      አሁንለታ ዑራኤል  ሰፈር አካባቢ ከምሽቱ አንድ ሰዓት እንዳለ በለቅሶ ቤት ድንኳን ውስጥ ሆነው ኀዘንተኞችን ሲያጽናኑ የነበሩ ሰዎችን ረጋግጦና በኃይል ገፍትሮ ወደ ውስጥ የዘለቀው ጅብ ይህን እስኪያደርግ ማንም ከውሻ የዘለለ ግምት  የሰጠው አልነበረም። ድምፁንና  ኮቴውን አጥፍቶ «ደህና አመሻችሁ?» በሚል አቀራረብ  ድንገት ዘው ያለው አያ ጅቦ  በገባበት ለመውጣት ተቸግሮ ሲደናበርም ብዘዎችን በድንጋጤና በጨኸት አተረማምሷል።

       አሁን አሁንማ የዚህ የጅብ ነገር ብርቅ መሆኑ ሊቀር ይመስላል። በቅርቡም ከአንዲት ወይዘሮ መኖሪያ ድንገት ብቅ ያለው የቀን ጅብ አካላቸውን ነካክሶና ለከፋ ጉዳት ዳርጎ እብስ ማለቱ አይዘነጋም። ኧረ መች ይሄ ብቻ ባለፈው አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት ሠፈር  የሆነውስ  የሚረሳ ነው እንዴ?  ይኼኛው ደግሞ ከየት እንደመጣ ባይታወቅም ካያቸው ቤቶች  ይበልጥ የማረከው ግን   አንድ  የጋራ መኖሪያ ግቢ  ነበር። አጥሩን አልፎ በዓይኑ ሲያማትርም እንደነገሩ ገርበብ ያለ ባለ አንድ መኝታ  ባዶ ቤት ይመለከታል።

       ግቢውን አልፎና ደረጃዎቹን ወጥቶ ወደ ውስጥ  ሲዘልቅም ማነህ? ወዴት ነህ? ያለው አልነበረምና  ከንጋት እስከምሽት ሲያሻው ከመኝታ ቤት ሲለው ደግሞ ከሳሎን ወደ መታጠቢያ እየተንሸረሸረ ጊዜውን አሳልፏል።  ቆይቶ የአያ ጅቦ በቤቱ መኖር ሲረጋገጥ ደግሞ ለማምለጥም ሆነ በፈቃደኝነት ለመውጣት  አልፈለገም። ቤቶቹ ለባለቤቶቹ በዕጣ የተከፋፈሉ የሰዎች መኖሪያ እንጂ የጅብ ዋሻ አለመሆኑን ያልተረዳው ጅቦ  በተለያየ ዘዴ እንዲወጣ ጫና  ቢደረግበትም ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል። ይህን  ማለቱ ደግሞ ቆይቶም ቢሆን የህይወት ዋጋ አስከፍሎታል።

     እንደው እናንተዬ  የዘንድሮ ጅቦች  ማንነታቸውን ዘነጉት ልበል? ጫካውን  ጠልተው፣ ዋሻ ጉድጓዳቸውን ትተው በከተማው መብራት መንሸራሸርን እስቲ ምን ይሉታል? ደግሞ ከሁሉም የሚገርመው ለመኖሪያ የሚመርጡት ቤት ኮንዶሚኒም መሆኑ። ወይ ጉድ! ዕጣ እንደደረሳቸው ባለመብቶች እኮ ቤቶችን እየከፈቱ የእኔ ነው ማለትን ጀመሩ ማለት ነው። ከዓመታት በፊትም እንዲሁ በሃያት የጋራ መኖሪያ ቤቶች በአንዱ በረንዳ ላይ የተገኘው ጅብ የትኛውን ቤት እንደፈለገ ባይታወቅም ካለበት ሆኖ ሲያደባ እጅ ከፍንጅ ተይዟል። እኔ ግን ወዳጆቼ  የነዚህን ጫካ ለምኔ እንግዶች ወደ ሰዎች ጠጋ ጠጋ ማለትን አልወደድኩም።

     አያ ጅቦ ሆይ! እኛ ሰዎች  ምን እንተርታለን መሰለህ? «ጅብ በማያውቁት ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ  ይላል» ብለን። አየህ እኛ  ማን መሆንህን  ጠንቅቀን  እናውቃለን ማለት ነው። አንተም  ብትሆኑ እኮ ይህ የሚጠፋህ አይመስለኝም። ስለዚህ ወዳጅነትህን በፍጹም አንሻም። ደግሞም አልደረስንብህምና አትድረስብን። በቃ! አያ ጅቦ እንከባበር !!

 

መልካምሥራ አፈወርቅ

Published in መዝናኛ
Wednesday, 08 February 2017 20:04

በቆሸሹ እጆች...

በርካታ ሴቶች ለከተማችን ጽዳት እንዲህ ይተጋሉ፤

 

ከሌሊቱ መጋመስ በኋላ በዓይኖቻቸው ዕንቅልፍ የሚባል ዝር አይልም። ለእርሳቸው ይህ ሰዓት ማለት የመተኛ አይደለም። ነቅቶ የመጠበቂያ እንጂ። የወይዘሮዋ ዓይኖች የጠዋቷን ጀምበር መውጣት ሳይሆን የለሊቷን ጨረቃ መድመቅ ይናፍቃሉ። በእርሳቸው ልማድ ከውድቅት በኋላ ዕንቅልፍ ይሉት ነገር አይሞከርም። ጎህ ሲቀድና ዶሮ ሲጮህ ጠብቆ መንገድ መጀመርንም አያውቁትም። ይህንንም ህይወት ላለፉት በርካታ ዓመታት ተለማምደውታል።

መንደራቸው በእጀጉ ያስፈራል። የመንገዱ ጨለማነትና የእርሳቸው ብቸኝነትም ሌላው ስጋት ነው። በተለምዶ ፈረንሳይ 41 እየሱስ ከሚባለው ሰፈራቸው ተነስተው አራት ኪሎ ለመድረስ ደግሞ በአካባቢው ያለውን የሀምሌ 19ኝን መናፈሻ ማቋረጥ ግድ ይላቸዋል። በዚህ መንገድ ጅብና ሌሎች የዱር አውሬዎች ሊገጥሟቸው ይችላሉ። ይህ እንደሚሆን ደግሞ ወይዘሮ ፍቅርተ መንገሻ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ግን በዚህ ሰዓት የሚጓዙበትን ትራንስፖርት መናፈቅ ዘበት ነውና ሌላ ምርጫ የላቸውም።

ልክ ከለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል መንገድ የሚጀምሩት ወይዘሮዋ 11 ሰዓት ሳይሞላ ሥራ መድረስ ይኖርባቸዋል። ይህ እንዲሆንም ከዕርምጃ ፈጠንና ነጠቅ እያሉ መጓዝ ግድ ነው። መንገደኞች ሳይወጡና መኪኖች ሳይበረክቱ እርሳቸውና መጥረጊያ ተገናኝተው የጎዳናው ፅዳት መጀመር አለበት። ፍቅርተ በፍራቻ ግራ ቀኙን እየቃኙ፣ኮሽታና ጭርታውን እየለዩ ይጓዛሉ። መንገዳቸው ሰላም ከሆነና ምንም ካልገጠማቸው አምላካቸውን ሲያመሰግኑ ይውላሉ።

ብዙ ጊዜ ሰፈራቸውን አለፍ ብለው ዋናውን ጎዳና ሲጀምሩ ጅቦች ያጋጥሟቸዋል። ይህ ሲሆን ደግሞ ከመደናገጥ ይልቅ የራሳቸውን ዘዴ ተጠቅመውና እነርሱን አግባብተው ማለፉን ለምደውታል። እርሳቸው እንደሚሉት አንድን ጅብ በጸባይ ካናገሩትና ካልተተናኮሉት ገራምነቱ ያደላል። ለእርሳቸው ከጅቦቹ ይልቅ እጅግ የሚያስደነግጣቸውና ሁሌም የሚያስፈራቸው ቢኖር በለሊት ለዘረፋ የሚወጡ ሌቦች ናቸው። እነርሱንም ቢሆን እንደ ልጆቻቸው የእናት ሰላምታ ሰጥተውና ተግባብተው ያልፏቸዋል። ሆኖም ሁሉም አንድ ሰላልሆኑና ቀኖች ሁሉ ሙሉ ስለማይሆኑ በዚህ ዘዴያቸው እምብዛም አይተማመኑም። ይሁን እንጂ ለዓመታት ባለፉበት የለሊት መንገድ አለባበሳቸው ለእይታ የሚጋብዝ ባለመሆኑ የከፋ የሚባል ችግር አልገጠማቸውም። ሌቦቹም ቢሆኑ ምንም የላቸውም በሚል እሳቤ ተሳስቀው ያልፏቸዋል።

ወይዘሮዋ በስጋትና በፍራቻ የተሞላውን የመንደራቸውን አካባቢ ካለፉ በኋላ ለተመሳሳይ ሥራ የሚወጡ ጓደኞቻቸው ስለሚቀላቀሏቸው ቀሪውን መንገድ በእፎይታ ይጓዛሉ። ይሁን እንጂ ኑሮን ለመምራትና ቤተሰብን ለማስተዳደር ነገም ተመልሰው ያንን አስፈሪ መንገድ እንደሚያልፉት ሲያስቡ እንደ ሰው ይጨነቃሉ። ጥንካሬና የተለየ ብርታት የተቸራቸው ሴት ግን ምንጊዜም ነገን ለራሱ ትተው ዛሬን በብቃት ማሸነፍን ተክነውታል። ሁሌም ለሥራ የማይሰንፉ የቆሸሹ እጆቻቸው ቆሻሻን ጠርገው ብር መቁጠሩን አላቆሙምና።

የአምስት ወንዶች ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ፍቅርተ 45 ዓመታትን በአዲስ አበባ ሲኖሩ 32ቱን ዓመት በፅዳት ሥራ አሳልፈዋል። በእነዚህ ጊዜያት ቤታቸውን ያስተዳደሩትና ልጆቻቸውን አስተምረው ለወግ ማዕረግ ያበቁት በዚሁ ሙያ በመሆኑ ለሥራቸው የተለየ ፍቅር አላቸው። ወይዘሮዋ በእነዚህ ፈታኝ የሥራ ዓመታት በየጊዜው የሚታከልላቸውን የደሞዝ ጭማሪ አካቶ አሁን አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ይከፈላቸዋል። ከዚህ ሁሉ ረጅም የአገልግሎት ዘመን የበረታ ልፋትና ድካም በኋላ ይህ ደሞዝ በቂ ነው ብለው አያምኑም። ይሁን እንጂ እንጀራ ያበሏቸውን የቆሸሹ እጆቻቸውን ዛሬም አውሎ ያገባላቸው ዘንድ ለአምላካቸው ምስጋና ከመቸር አይቦዝኑም። የእርሳቸው እጅ መቆሸሽ ለሌሎች መንፃት ምክንያት መሆኑ ሲታወሳቸውም የምስጋናቸውን ደረጃ ከፍ ያደርጉታል።

ወይዘሮ ፍቅርተን ሁሌም የሚያናደዳቸው ነገር ቢኖር የአብዛኛው ህብረተሰብ የቆሻሻ አጠቃቀም ግንዛቤው ማነስ ነው። በሥራ አጋጣሚያቸው በየመንገዱ የሞቱ አህዮች፣ ውሾችና ሌሎች እንስሳትን ከማስወገድ ባለፈ በሰዎች ግዴለሽነት ያለአግባብ የሚጣል ቆሻሻን ሳይጠየፉ ሲያነሱ ኖረዋል። የእንስሶቹ መውደቅ በአብዛኛው የአደጋ አጋጣሚ መሆኑን ቢያምኑበትም አንዳንድ ሰዎች የሚፈጽሙት ያልተገባ ድርጊት ደግሞ ሁሌም ያበሳጫቸዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ እነዚህ ሰዎች ከራሳቸው ጥቅም ውጪ ስለሰው ክብር የሚጨነቁ አይደሉም። ቤታቸው ሊፈጽሙት የማይወዱትን ሁሉ ጎዳናውና የፅዳት ባለሙያዎች ይቻሉት በማለትም በቃላት ሊገለጹና ሲያዩዋቸው የሚያሳፍሩ ጉዳዮችን ሳይቀር አውጥተው ይወረውራሉ። ምንም እንኳን እርሳቸውና ባልደረቦቻቸው እንጀራቸውን የሚያከብሩና ሙያቸውን የሚወዱ ቢሆኑም ይህ ዓይነቱ ድርጊት ደግሞ በእጀጉ ያሳዝናቸዋል። ወይዘሮ ፍቅርተ የዓመታት የፅዳት ሥራቸው ብዙ ቢያሳያቸውም ከመማረር ይልቅ ሠርተው ፍሬያማ መሆን ደግሞ ዕምነታቸው ነው። አልፎ አልፎ ለፅዳት የሚረከቧቸው ጓንቶች ሲያልቁ በእጆቻቸው ላይ የሚያጋጥማቸው ጉዳት ደግሞ የከፋ እንደሚሆን ይናገራሉ። በዘወትር ሥራቸው የሚገጥማቸው ችግር በዚህ አያበቃም።

በዚህ ሥራ ወድቆ መሰበር፣ በስለት መቆረጥና በድንጋይ መቀጥቀጥ በሙያው ባለፍኩበት ዓመታት መደበኛ የሥራው ሳንካዎች  ናቸው። በቅርቡም በጨለማ ከጉድገድ የተጣለ ቆሻሻን ለማንሳት ሲሞክሩ ባጋጠማቸው ስብራት በወጌሻ ታሽተው ስለ ማገገማቸው አልደበቁም።

በተቀዳደደው የእጅ ጓንት መሀል ሾልከው የወጡትን የወይዘሮዋን ጣቶች አንድ በአንድ ዳሰስኳቸው። በእጅጉ ሻክረዋል። ስብራት ያጋጠመው አንደኛው እጅም የጉዳት አሻራው በግልጽ ያስታውቃል። ዛሬም ቢሆን ግን ለሥራም ሆነ ለተለመደው ጥንካሬ መዛል አይታይበትም። በጉንፋን የከረመው አፍንጫቸውን ጨምሮ መላውን ፊታቸውን ሸፋፍነው ደፋ ቀና የሚሉት ወይዘሮ ፍቅርተ፤ ዓውደ ዓመትን እንደማንኛውም ሰው በአግባቡ ቤታቸው እንደማያሳልፉ ይናገራሉ። በተለይ የበዓል ሰሞን ከየቤቱ የሚወጣው ቆሻሻ ጠንከር ያለ ህመም ትቶባቸው ያልፋል።

ሁሌም የውሎ ግዴታቸውን ፈጽመው ቤታቸው ሲደርሱ ደግሞ ለጡረተኛው ባላቸውና ለመላው ቤተሰብ ጭምር ቀሪውን ኃላፊነት የመወጣት ግዴታ ይቆያቸዋል። ሆኖም ግን የቀኑም ሆነ የለሊቱ ድካም ፈጽሞ አማሯቸው አያውቅም። የዛሬው ጥንካሬ ለነገው ብርታት ሆኗቸዋልና ሙያቸውን አክብረውና እንጀራቸውን ፈቅደው የመኖር ቁርጠኝነትን መሰነቅ መለያቸው ሆኗል። አንጋፋዋ የጎዳና ፅዳት ባለሙያ ወይዘሮ ፍቅርተ መንገሻ።

ዘወትር ለሊት ዘጠኝ ሰዓት ከመኖሪያዋ ወጥታ የአስፓልቱን መንገድ ትጀምራለች። ይህ ሰዓት ለፅዳት ባለሙያዋ ጠጅቱ ኡካ ሁሌም የተለመደ ነው። በታሰበው ጊዜ ቦታው ካልደረሰች ደግሞ ገንዳ ጭኖ የሚወጣው የቆሻሻ መኪና ሊያመልጣት ይችላል። ለገንዳው ሆድ መሙላት የእነጠጅቱ ጋሪዎች መኖር ወሳኝ ነውና ከእነርሱ ጋር እየታገሉ በማዳበሪያ ተጠቅጥቆ የታጨቀውን ቆሻሻ ወደ መኪናው ማጋባት የግድ ይላል።

ወይዘሮ ጠጅቱ ሰዓቷን አክብራ ከሥራ ገበታዋ ለመገኘት ስትል ብዙና ፈታኝ የሚባሉ አጋጣሚዎችን አልፋለች። ለእንጀራዋ የተለየ ክብር በመስጠቷም ፈተናዎችን መጋፈጥ ልማዷ ነው። የዛን ዕለታው ለሊት ግን ለፅዳት ባለሙያዋ ጠጄ ምንጊዜም የማይረሳ ነበር። እንደተለመደው ጨለማውን አልፋ የአስፓልቱን መንገድ እንደጀመረች ሁሌም በጭርታ የሚቀበላት ጎዳና በዚያን ለሊት ብቻውን አልነበረም። ከመንገዱ ጥግ ተቀምጦና የእርሷን መድረስ አድብቶ ይጠብቅ የሚመስለው የአዕምሮ ህመምተኛ ጠጄን እንዳያት ከተኛበት እመር ብሎ ወደእርሷ ሮጠ።

ድንገት የያችው ጠጄም ፈጥና ለመሮጥም ሆነ በፍጥነት ለማምለጥ ዕድሉ አልነበራትም። ሰውዬው በእጁ እንደገባች በያዘው ዱላ እያገላበጠ ይገርፋት ጀመር። ገላጋይና ታዛቢ በሌለበት በዚያ ውድቅት ጠጅቱ ደጋግማ የድረሱልኝ ጨኸትን አሰማች። በቀላሉ ከእጁ የወደቀችለት ህመምተኛ ግን ጩኸቷን ሲሰማ ከመደናገጥ ይልቅ ምቱን አጥብቆ ድብደባውን ያበረታባት ያዘ። አጋጣሚ ሆኖ በስፍራው ይዘዋወሩ የነበሩ ፖሊሶች ደርሰው ጠጅቱን ከነበረችበት ችግር ታደጓት።

ይህ ታሪክ የጠጅቱ ብቻ አይደለም። ይህ እውነት በዚህ ሥራ ተሰማርተው የሙያ ግዴታቸውን የሚወጡ የብዙዎቹ የጎዳና ላይ ፅዳት ሠራተኞች ታሪክ ነው። ወይዘሮ ጠጅቱ በእርሷ ላይ እስከአሁን ያጋጠማት ዝርፊያ የለም። የሥራ ባልደረቦቿ ግን በተለያዩ ጊዜያት ኪሳቸው እየተፈተሸ ገንዘብና ሞባይላቸውን በለሊት ቀማኞች ተነጥቀዋል። ጠጄ ለአስር ዓመታት ያህል ገንዳ ላይ ቆሻሻን በመጫንና ከባዱን ጋሪ በመግፋት አሳልፋለች። በዚህ ሙያ ላይ እያለችም ጋሪው ወደ ኋላ እየተመለሰ በጉልበቶቿ ላይ ተደጋጋሚ ጉዳት አድርሶባታል። ለብዙ ጊዜም ያለ ጥንቃቄ በተጣሉ ስለታማ ነገሮችና ጠርሙሶች እጆቿ የመቆረጥ አደጋ አጋጥሟቸዋል። ጠጄ ከአራት ዓመት ወዲህ ባገኘችው የውድድር ዕድልና የተሻለ ክፍያ ምክንያት የጎዳናን ፅዳት መሥራት ጀምራለች።

አሁን መኖሪያዋ ቅርብ በመሆኑና ባለቤቷም አብሯት ስላለ የትናንቱ የፍራቻ ጉዞ አይጠብቃትም። ጠጄ ለእንጀራዋ ስትል የምትከፍለው ፈተና ባያስከፋትም አንዳንድ ሰዎች ለሥራውና ለሠራተኞቹ ያላቸው ግምት ማነስ ደግሞ በእጅጉ ያስገርማታል። እርሷ እንደምትለው እነዚህ ሰዎች ከሚጥሉት ቆሻሻ ይልቅ የሚጠየፉት የፅዳት ባለሙያዎቹን በመሆኑ ሲጠሯቸው እንኳን «ቆሻሻዎች መጡ» በሚል ስያሜ ነው። እርሷና ጓደኞቿ ግን ቆሻሻን ጠርገው ልጆች ያስተምራሉ። ቆሻሻን አንስተው ቤታቸውን ይመራሉ። የቆሸሹ እጆቻቸው ለእነርሱ የእንጀራቸው መቁረሻ፣ የህይወታቸው መነሻና መድረሻም ናቸው።

የጠጅቱ ሥራ በቀን ውሎ የሚከወን ባለመሆኑ ማህበራዊ ግዴታዎችን ለመወጣትና በተጨማሪ ሥራዎች ለመሳተፍ እንደሚቸግራት ትናገራለች። ይሁን እንጂ ዕንቅልፍ እያዳፋትም ቢሆን በዕድሩም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ከመሄድ ተቆጥባ አታውቅም። ጠጄ ሁለት ወንድ ልጆቿ ተማሪዎች በመሆናቸውና ኃላፊነቱ ስላለባት እነርሱን ለማስደሰት የአቅሟን ታደርጋለች። የሚከፈላት ደሞዝ በቂ ነው ባትልም ከባለቤቷ ገቢ ጋር በማዳመር ደስተኛ ህይወትን እየመራች ነው። ከሁሉም ደግሞ የሥራ ውጤቷን ስታይ ከፍ ያለ እርካታ ይሰማታል። ምንም እንኳን ሥራው ፈታኝና ጥንካሬን የሚጠይቅ ቢሆንም እራስን ማሳመኑ ከታከለ ከዚህም ይበልጥ ሠርቶ ፍሬያማ መሆን እንደሚቻል ዕምነቷ ነው።

ልክ እንደ ወይዘሮ ፍቅርተና ጠጅቱ ኡካ ሁሉ ቆሻሻን ጠርገው ህይወትን የሚመሩ፣ ሌሎች ለማየት የሚጸየፉትን አንስተው እንጀራን የሚቆርሱ፣ ለአፍንጫ የሚከብድ ክፉ ሽታን ተቋቁመው ለሌሎች ጤናን የሚዘሩ ዜጎች ዕልፍ ናቸው።

Published in ማህበራዊ

የሞባይል ስልክ ቀፎ መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች በኢትዮጵያ፤

ቻይና በጀኔራል ማኦ መሪነት  እ.ኤ.አ በ1949 ‹People Republic of China› ተብላ ከተመሠረተች በኋላ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው እና በማህበራዊ ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ ዕድገት አስመዝግባለች፡፡ እኤአ ከ1953 ጀምሮ 13 የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ  አቅዳ አሳክታለች፡፡ በተለይም በመጀመሪያው የእቅድ ዘመኗ (1953 እስከ1957) 694 ትላልቅና መካከለኛ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶችን መተግበር ችላለች፡፡ አሁን ላለችበት የዕድገት ደረጃም በዚያን ዘመን የጣለችው መሠረት እንደሆናት ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ኢትዮጵያም በአንደኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የዕድገቱ ዋና ምንጭ የግብርናው ዘርፍ እንደሚሆን፤ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ደግሞ ከግብርናው ዘርፍ በላቀ ፍጥነት በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለመሸጋገር የሚያስችል ሀብት እንዲፈጥር አቅዳ ተንቀሳቅሳለች፡፡ ሆኖም እቅዱ እንደሚጠበቀው ግቡን ሳይመታ ቀርቷል፡፡

የኢንዱስትሪው ዘርፍ በ2003 ዓ.ም ከነበረው የ11 በመቶ ድርሻ ወደ 14 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ነገር ግን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው በአማካኝ በየዓመቱ በ13 በመቶ ዕድገት ቢያሳይም በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ድርሻ ግን ምንም ለውጥ ሳያመጣ በአምስት በመቶ ብቻ ተወስኗል፡፡

የኢንቨስትመንት መጠን ከጠቅላላው የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ በ2003 ዓ.ም ከነበረበት 32 ነጥብ አንድ በመቶ በ2006 ዓ.ም ወደ 40 ነጥብ ሦስት በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡አገራዊ የኢንጂነሪንግ እና ፋብሪኬሽን አቅምን በማሳደግና የአምራች ዘርፎችን ምርታማነትና፣ ጥራትና ተወዳዳሪነትን በማጎልበት የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግርሩን በማጎልበት ላይ ግን የታሰበውን ያህል መሄድ አልተቻለም፡፡

አሁን በተጀመረው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን በየዓመቱ ቢያንስ የ24 በመቶ ዓመታዊ አማካይ ዕድገት እንዲያስመዘግብ በማድረግ በ2012 ዓ.ም የማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ክፍሉ ከጠቅላላው የኢኮኖሚ ድርሻው ከነበረበት 5 በመቶ ወደ 8 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ ያላቸው ድርሻ ከ10 በመቶ አይበልጥም። ይህን ከፍ በማድረግ በ2012 ወደ 3 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ግብ ተጥሏል፡፡ አሁን ላይ በአምራች  ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የተሰማራው የሰው ኃይልም ከ350 ሺ የማይበልጥ ነው፡፡ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ግን ይህንን ቁጥር ወደ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዷል፡፡

ለአምራች ኢንዱስትሪው አስተፅኦ ከሚያበረክቱ ዘርፎች መካከል የሣይንስና  ቴክኖሎጂው ዘርፍ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍም፤ «በ2017 ሀገራችን ውጤታማ የሆኑ የውጭ ቴክኖሎጂዎችን በፍጥነት የመማር፣ የማላመድ እና የመጠቀም አቅሟ ተገንብቶ ማየት» የሚል ራዕይ ተይዟል፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ግን በተያዘው የእቅድ ዘመን ላይ ሆነው ሠፊ ችግር እዳለባቸው እየገለጹ ናቸው፡፡

የዊጎ ዮ ቴክኖ ሞባይል ዳይሬክተር አቶ ገነነ አዘነ፤ መንግሥት ለአምስት ዓመት ከውጭ ለሚያስገባቸው ዕቃዎች  የግብር እፎይታ ጊዜ ሰጥቷቸው ድርጅታቸው ተጠቃሚ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ «ነገር ግን ከሦስት ዓመት በፊት ቦሌ ለሚ በሚገኘው የአይሲቲ ፓርክ ውስጥ ቦታ ቢሰጠንም የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር እስከአሁን ህጋዊ የሆነ ማረጋገጫ ስላልተሰጠን ወደሥራ መግባት አልቻልንም» ሲሉ ቅሬታቸውን ያነሳሉ፡፡

ለተሰጣቸው ቦታ ህጋዊ ሰነድ ለማግኘት ከሦስት ዓመት በላይ እንደፈጀባቸው የገለጹት አቶ ገነነ፤ ህጋዊ የሆነ ዶክመንት ቢሰጣቸው ድርጅታቸው የ20 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ለመገንባት እቅድ መያዙን ገልጸዋል፡፡ ይህ ፕሮጀክት እውን ቢሆን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ገበያም ጭምር የሚተርፍ ምርት የሚመረትበት እንደሚሆንም ነው የሚናገሩት፡፡« ባለፉት ሁለት ዓመታት ሁለት ሚሊዮን 184ሺ ቀፎዎችን ወደ ውጭ በመላክ  25ሚሊዮን 544ሺ 412 ዶላር አግኝተዋል»።  ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ ቢገባ በሁለተኛው ትራንስፎርሜሽን እቅድ 300ሚሊዮን ዶላር ምንዛሬ ማስገባት  እቅድ እንዳላቸው አክለዋል፡፡

በተጠቀሰው የቦታ ችግር ምክንያት ላላስፈላጊ ወጪ እየተጋለጡ መሆናቸውን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ አሁን በኪራይ እየሠሩባቸው ያሉ ሁለት ቦታዎችም በከፍተኛ ሁኔታ የውሃ እጥረት ያለበትና የምርት ሂደቱን ፈተና ውስጥ የጣለ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ በተለይም የ20 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክቱን ለማስጀመር የቦታው ህጋዊ ሰነድ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን ቢጠይቁም ሊሰጣቸው እንዳልቻለ አልሸሸጉም፡፡

በኮንትሮባንድ የሚገቡ የስልክ ቀፎዎችም ለአገር ውስጥ የሞባይል ቀፎ አምራቾች ፈተና እንደሆነባቸው አቶ ዘገየ ተናግረዋል፡፡ «አሁን ጥቅም ላይ ከዋሉ የስልክ ቀፎዎች ውስጥ 64 በመቶው በኮንትሮባንድ የገቡ የስልክ ቀፎዎች ናቸው፡፡ ይህ በሥራችን ላይ ትልቅ ጫና እየፈጠረብን ነው» ብለዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃም ከግብር ክፍያ ጋር በተያያዘም ዘርፉ ትልቅ ተግዳሮት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩን ሲያስረዱም፤ ስልኩን ለማምረት አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ከመደበኛው በላይ ከፍተኛ የሆነ ታክስ ስለሚከፈልባቸው በምርት ዋጋ ተወዳዳሪ መሆን እንዳላስቻላቸው ነው የገለጹት፡፡ 

ወይዘሮ በላይነሽ ወረኛ በጣና ኮሙኒኬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባኒያ ውስጥ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንዳሉትም፤ ኩባንያው ሲመሠረት መንግሥት የማምረቻ ቦታ፣ የመብራት፣ የውሃና የመንገድ መሠረተልማቶችን በነፃ አሟልቷል፤ ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ ፈቅዶላቸዋል፡፡ በዚህም ሥራቸው የተሳለጠ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

አሁን ላይ የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ እጥረት እደገጠማቸው ይናገራሉ፡፡ «ምርቱን ለማቅረብ ተስማምተን ማቅረብ አልቻልንም፡፡ ብሄራዊ ባንክ ቅድሚያ የምናገኝበትን ሁኔታ ቢያመቻችልን የሚል ጥያቄ አቅርበናል፡፡ የምናስገባቸው ዕቃዎች እና ምርቶች ብዛታቸውና ዓይነታቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ በመሆኑም የምናገኛቸው የመንግሥት ድጋፎች በአጠቃላይ የእሴት ጭማሪውን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ድጋፍ እዲሆንልን እንፈልጋለን» ብለዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጇ ገለጻም፤ በሀገር ውስጥ ገበያ በዋጋ ተወዳዳሪ ለመሆንም ወደሀገር ውስጥ የሚያስገቧቸው የሚገጣጠሙ የስልክ አካላት ላይ የሚጣለው ታክስ ቅናሽ መደረግ አለበት፡፡

የህዳሴ ሞባይል እና ቴሌቪዥን ማምረቻ ድርጅት ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አንቶኒ ዦ በተመሳሳይ ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ጋር ተመሳሳይ ችግር እንዳለባቸው ገልጸው፤ በውጭ ሀገር ተመርተው ወደሀገር ውስጥ ከሚገቡት የሞባይል ቀፎዎች ጋር ተወዳዳሪ መሆን እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡   በሀገር ውስጥ ከሚገጣጠሙት ቀፎዎች በኮንትሮባንድ ከሚገቡ ቀፎዎችና በውጭ ሀገር ተገጣጥመው ቀጥታ ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገቡ ቀፎዎችም ባነሰ ዋጋ ንዲቀርቡ ካስፈለገ የታክስ ቅናሽ ሊደረግ ይገባል የሚል አስተያየት አላቸው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን በኮንትሮባንድ የሚገቡ የሞባይል ቀፎዎች በሀገር ውስጥ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን አልቻልንም ብለዋል፡፡

በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን የአይ ሲቲ ቪሌጅ ኮርፖሬሽን ዳይሬክቶሬት አቶ ብርሃነ ቀለታ፤ በቴክኖ ሞባይል በኩል ከቦታ ሰነድ ጋር ተያይዞ የተነሳውን ቅሬታ እንደሚያውቁት ይናገራሉ፡፡ ለቦታው ህጋዊ ሰነድ ለመስጠት ሦስት ዓመት መቆየቱንና ረጅም  ጊዜ መሆኑንም ያምናሉ፡፡ ዳይሬክተሩ አያይዘውም በአሁኑ ወቅት ሥራው እየተሠራ ስለሆነ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ካርታው ተሠርቶ እዲቀርብላቸው ይደረጋል ብለዋል፡፡

በገቢዎች እና ጉሙሩክ ባለሥልጣን የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን በኮንትሮባንድ  የሚገቡ የስልክ ቀፎዎችን እንደሌሎች የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ሁሉ፤ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከክልል የፀጥታ አካላትና የክልል የሚሊሻ ፖሊሶች  ጋር በመሆን የመከላከል ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ኤፍሬም፤ ገቢዎች እና ጉሙሩክ ብቻውን ይሄን መቆጣጠር እንደማይችል ገልጸው፤ እስከአሁንም ከተጠቀሱት ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሞባይል ቀፎዎች ውርስ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ይሄንን የቁጥጥር ሥራ እዲያግዝም የሚያሸልም የጥቆማ ስርዓት ተዘርግቶ እየተሠራ መሆኑንና አበረታች ለውጥ መታየት መጀመሩን አብራርተዋል፡፡ 

አምራቾቹ በአገር ውስጥ ለሚያመርቷቸው የስልክ ቀፎዎች በግብአትነት በሚውሉ ዕቃዎች ላይ ልዩ የታክስ ቅናሽ እንደሚደረግም አቶ ኤፍሬም ጠቁመዋል፡፡ በኮንትሮባንድ የሚገቡ ስልኮችን ጫና ለማስቀረትም መንግሥት የአንድ ሲም አንድ ቀፎ አገልግሎትን (ኢንተግሬትድ አይፒ ሬጅስትሬሽን)  ለመጀመርና በህጋዊ መንገድ ታክስ ለተከፈለባቸው የስልክ ቀፎዎች ብቻ የስልክ ኔትወርክ ለመስጠት የሚያስችል ቴክኖሎጂን ለመተግበር ማቀዱ ይታወቃል፡፡ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ መረጃ እንዲሰጠን የጠየቅነው ኢትዮ ቴሌኮም ፈቃደኛ አልሆነም፡፡

ከውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ኩባንያዎቹ ያነሱት ጥያቄም ተገቢ መሆኑ በመንግሥት በኩል ይታመናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያም፤ አገሪቷ ከገባችበት ፈጣን ዕድገት ጋር በተያያዘ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎቱ መጨመሩንና መንግሥት ያለውን ክምችት እንደ ዘርፎቹ አንገብጋቢነት እየለየ እንደሚያቀርብ በተለይ ግን ለአምራች ኢንዱስትሪው ቅድሚያ እንደሚያገኝ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

አየናቸው እሸቱ

Published in ኢኮኖሚ

 

እሥራኤል ለማካሄድ ያቀደችው የሰፈራ መርሐ ግብር እያወዛገበ ነው፤

 

ሰላም እንደ ውሃ የጠማው አካባቢ ነው - መካከለኛው ምሥራቅ። አንዴ ሞቅ አንዴ ደግሞ ቀዝቀዝ እያለ ውዝግብና ውጥረት ተለይቶት አያውቅም። በዚህ አካባቢ የሽብር ተግባርም እንግዳ ነገር አይደለም። በዚህ በቋፍ ላይ ባለ  አካባቢ ነው «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» እንዲሉ  ሰሞኑን  የእሥራኤልና የፍልስጤም የሰላም ሂደትን ሊያጨናግፍ የሚችል የሠፈራ መርሐ ግብርን  ህግን በ60 ድጋፍ በ52 ተቃወሞ በአብላጫ ድምፅ  የእሥራኤል ፓርላማ ያፀደቀው።

የእሥራኤል ፓርላማ 4ሺ ቤቶችን በዌስትባንክ ዳርቻ መገንባት የሚያስችለው አወዛጋቢ ህግ በድምፅ ብልጫ ያፀደቀው ባለፈው ሰኞ  ነው። የሠፈራ መርሐ ግብሩ በሚካሄድበት አካባቢ የመሬት ባለቤት የሆኑ ፍልስጤማዊያን  በመሬታቸው ምትክ የገንዘብ ካሣ ወይም ምትክ ቦታ እንደሚሰጣቸውም ታውቋል።

የእሥራኤል የሠፈራ መርሐ ግብር የሰላም ሂደቱ ላይ መሰናክል ይፈጥራል በሚል በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ  ውግዘትን አስከትሎበታል። የቀድሞው የኦባማ አስተዳደር  እሥራኤል ለማካሄድ ያቀደችውን የሠፈራ መርሐ ግብር በግልጽ ሲያወግዝ በአንፃሩ አዲሱ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ  አስተዳደር ለእሥራኤል ያለው ጠንካራ ድጋፍ የተነሳ የሠፈራ መርሐ ግብሩን እንደማይ ቃወመው ይፋ አድርጓል።

በመቶ የሚቆጠሩ የአይሁድ ሠፈሪዎች በዌስትባንክ የደህንነት ችግር እንዳያጋጥማቸው የእሥራኤል የፀጥታ ኃይሎች አስፈላጊውን ጥበቃ እያደረጉ ይገኛሉ። በፍልስጤም መሬት ላይ የሚደረገው አወዛጋቢው የሠፈራ መርሐ ግብር ዳግም በአካባቢው ቀውስ እንዳይቀሰቅስ ተፈርቷል። የእሥራኤል  ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቨቻ ማነደለበለት እንደገለጹት ህጉ ህገ መንግሥታዊ አይደለም፤ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱም አልቀረበም ብለዋል።

የእሥራኤል የካቤኔ ሚኒስትሩ ኦፈር አኩኒስ በበኩላቸው እንደተናገሩት «ለህጉ ድምፅ ሰጥተን እንዲፀድቅ ያደርግነው ከእሥራኤል ህዝብና መሬት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ስላለው ነው። የሠፈራ መርሐ ግብሩ የሚካሄድበት  መሬትም የእኛ ነው።»

ፍልስጤም ህጉን ኮንናዋለች

«ህጉ  በአካባቢው እንደገና ቀውስ እንዲቀ ሰቀስና  አለመረጋጋት እንዲፈጠር ያደርጋል» ያሉት ደግሞ የፍልስጤም አስተዳደር መሪ የማህሙድ አባስ ቃል አቀባይ ናቢል አቡሩዲነል ናቸው። ህጉ በፍልስጤም አስተዳደር ዘንድ ተቀባይነት የለውም። የዓለም አቀፉ ህብረተሰብም ሊያወግዘው ይገባል» ሲሉ ድርጊቱ ጠብ አጫሪነት በመሆኑ ኮንነዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ አደራዳሪ ሚስተር ኒኮላይ ማልዶኖቨ እንዳሉት ህጉ የአረብ- እሥራኤል የሰላም ሂደትን የሚያደናቅፍ ነው። እናም እሥራኤል ጉዳዩን ሰከን ብላ ብትመለከተው የተሻለ ነው ብለዋል።

እሥራኤል 6ሺ ቤቶችን በዌስትባንክና በእየሩሳሌም ለመገንባት በሠፈራ መርሐ ግብር ዕቅድ የያዘች ሲሆን ፣የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶላልድ ትራምፕ የእሥራኤል የቤቶች ሠፈራ መርሐ ግብሩ ለሰላም ሂደቱ ያን ያህል ጠቃሚ አይደለም ሲሉ አጣጥለውታል።

እኤአ በ1967  በተካሄደው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት  እሥራኤል ዌስትባንክንና ምሥራቅ እየሩሳሌምን ከያዘች ወዲህ በ140 የቤት ግንባታ ጣቢያዎች600ሺ እሥራኤላዊያን ሰፍረው እንደሚገኙ ይታወቃል። የሠፈራ መርሐ ግብሩም በዓለም አቀፍ ህግም ሆነ ማህበረሰብ ህጋዊ እንዳልሆነ ይጠቀሳል። በመካከለኛው ምሥራቅ የሰላም ሂደትም መሰናክል እየፈጠረ እንደሆነ ቢቢሲ የዜና ማሰራጫ ጣቢያ ዘግቧል።

የእሥራኤል የቤቶች ሚኒስቴር ኡሪ አርየል መንግሥታቸው በኃይል በያዘው የፍልስጤሞቹ ግዛት ዌስትባንክና ምሥራቃዊ እየሩሳሌም  አራት ሺ አዳዲስ የአይሁድ መኖሪያ ቤቶች ለማስገንባት መወሰኑን አስታውቀዋል።

ይህም ላለፉት 20 ዓመታት የእሥራኤል ፍስልጤም ድርድር እየተጀመረ ስለመቋረጡ እንደ ዋና ምክንያት ከሚጠቀሱት አንዱ እንደሆነ ይነሳል። እሥራኤል በኃይል በያዘችው የፍልስጤም ግዛት የአይሁድ ሠፈራ መንደር መገንባቷን አለማቆሟ  ለሰላም ድርድሩ መደናቀፍ መንስኤ መሆኑን  ተንተኞች ይገልጻሉ።

የፍልስጤም አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣን ያሲር አብድ ረቦ ያሉትም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው። አዲሱ የእሥራኤል የሠፈራ መርሐ ግብር ህግም ገና  በሂደት ላይ ያለውን የሰላም ድርድር ሊያደናቅፈው ይችላል። ፍልስጤም ሁሉንም የእሥራኤል ሠፈራ መንደሮች ሕገወጥነት መሆናቸውን ነው የምትቀበለው ሲሉ የእሥራኤልን የሠፈራ መርሐ ግብር አውግዘውታል።

እሥራኤል በዌስትባንክና በምሥራቅ እየሩሳሌም የምታካሂደው የሠፈራ መርሐ ግብር ለእሥራኤል-ፍልስጤም ግጭት እንደ ዋነኛ መንስኤ ይጠቀሳል። ፍልስጤም ወደፊት ለምመሠርተው አገር እነዚህ ስፍራዎች ግዛቴ ይሆናሉ ስትል በአንፃሩ እሥራኤል የእኔ ግዛቶች ናቸው በሚል የሠፈራ መርሐ ግብር እያካሄደችባቸው ትገኛለች። ይህ መርሐ ግብርም መጀመሪያ መቆም ይኖርበታል ስትል ፍልስጤም ለሰላም ድርድሩ እንደ ቅድመ ሁኔታ ታስቀምጠዋለች። ይህ የሠፈራ መርሐ ግብርም የፍልስጤማዊያንን ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብት ገድቧል። ምክንያቱም እሥራኤል ለደህንነት  ስትል ብዙ የፍተሻ ጣቢያዎችን አቋቁማለች። መንገዶችንም ዘግታለች። ለዚህም ነው መርሐ ግብሩ የእሥራኤል ፍልስጤም የሰላም ድርድር መቋጫ እንዳያገኘ አድርጓል ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች  የሚያብራሩት።

በተቃራኒው እሥራኤል የሠፈራ መርሐ ግብሩ ለሰላም ድርድሩ እንቅፋት አይሆንም ስትል ትሞግታለች። እውነት ፍልስጤም ለሰላም ድርድሩ ፅኑ ፍላጎት ካላት ይህን መርሐ ግብር እንደ ቅድም ሁኔታ ከማስቀምጥ ይልቅ በቀጥታ መደራደር ይቻላል በማለት መርሐ ግብሩ ለሰላም ድርድሩ መሰናክል እንዳልሆነ አስተባብላለች።

ተንታኞች እንደሚያስረዱት በዌስትባንክ የሠፈራ መርሐ ግብሩ ስምምነት ቢደርስ እንኳን የምሥራቅ እየሩሳሌም የሠፈራ መርሐ ግብር ግን የሚያጨቃጭቅና መፍትሔ አልባ ነው። ምክንያቱም እሥራኤል የማትከፋፈል እየሩሳሌም ዋና ከተማዋ ለማድረግ ፍላጎት አላት፤ የእምነት ስፍራዬ እንደሆነ መረጃ አለኝ ትላለች። በአንፃሩ ደግሞ ፍልስጤም እየሩሳሌም ዋና ከተማዬና የእምነት ስፍራዬ ናት ስትል በፀና አቋማን አሳውቃለች።

 

ጌትነት ምህረቴ

Published in ዓለም አቀፍ

በአፍሪካዊቷ ጋና የሚኖሩ አካን የተባሉ ጎሳዎች አሉ። የአካን ሰዎች ታዲያ እንደ ተቀሩት አፍሪካዊያን ሁሉ በተፈጥሮ ሀብትም ብቻ ሳይሆን በተረትና ምሳሌ ጭምር የበለጸጉ ናቸው። ነገራቸውን ሁሉ በምሳሌ አጅቦ መናገር የዚያ ጎሳ አባላት መለያ ባህሪ እንደሆነ ይነገርላቸዋል።

የአንድ አካን ጎሳ አባል አዋቂነቱ የሚለካውም በሚያውቀው ምሳሌ ብዛትና በንግግሩ መካከል እንደ ማጣፈጫም እንደ መልዕክት ማጠንከሪያም በሚጠቀማቸው ተረቶቹና ምሳሌዎቹ ብዛትና ዓይነት እንደሆነ የጎሳው ታሪክ ይነግረናል። (ወዲህ እኛ አገር በንግግራችን መካከል የእንግሊዝኛ ቃል ጣል እንደምናደርጋት ዓይነት መሆኑ ነው)፡፡

እነሆ ለዛሬ ከአካኖች አንድ ተረትና ምሳሌ ልዋስ ወደድኩ፤ «ከእናቷ ያልራቀች ጫጩት የፌንጣ ጭን ታገኛለች»የሚለውን። ልብ ብለው ያንብቡት፤ ያልኩት «ከእናቷ ያልራቀች ጫጩት የፌንጣ ጭን ታገኛለች»ነው።

ጫጩቷ የምታገኘው የፌንጣ ጭን ነው። የፌንጣን ብልት ማን ቆጠረው? ማንስ ገነጣጥሎ ዓይቶና ተረድቶ እንዲህ ሊባል ይችላል? ወደሚል ፍልስፍና ውስጥ አልገባም። ይልቁንም አካኖች ከዚህ ተረትና ምሳሌ ጀርባ ቀብረው ያስቀመጡት ቱባ መልዕክት ቀጥዬ ለማቀርበውና ለዛሬ ይዤው ለመጣሁት ሃሳብ ልኩ ስለሆነልኝ እሱን እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ። 

እንዳልኩዎት አካኖች «ከእናቷ ያልራቀች ጫጩት የፌንጣ ጭን ታገኛለች»የሚል ተረትና ምሳሌ አላቸው፡፡ የዚህ ተረትና ምሳሌ ሙሉ መልዕክቱም፤ አካኖች እንዳሉት፤ አንድ ሰው ራሱን ካገለለ ጥሩ ነገር በሚከፋፈልበት ጊዜ በቀላሉ ሊረሳና ሊታለፍ ይችላል የሚል ነው። ወዲህ በእኛ አገር «ላኩራፊ ምሳው እራቱ ነው» እንደምንለው ዓይነት መሆኑ ነው።

ለማንኛውም ይህ የአካኖች ተረትና ምሳሌ በትክክል ይገልጽልኛል ወዳልኩት ሃሳብ ልለፍ፡፡ በአንድ በኩል የመልካም አስተዳደር ችግር፤ በሌላ በኩል ደግሞ የውጭ ኃይሎች ፍላጎትና ድብቅ ዓላማ አንድ ላይ አብረውባት አገራችንን ወደ ቀውስ ውስጥ ከተዋት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ይህ ወቅት ለአገራችን በተለይ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ ከተከሰቱ ሁከቶች ሁሉ በዓይነቱም ብቻ ሳይሆን በአደገኝነቱም እጅግ ከባድ እንደነበር ችግሩን የተረዳው ሁሉ የሚያውቀው ሐቅ ነው፡፡ ምስጋና ለመንግሥትና ለህዝብ አገራችን እንድትገባበት ታቅዶላት ወደ ነበረው የጸጥታ ችግር አዘቅት ውስጥ ከመግባቷ በፊት ተርፋለች፡፡ 

በተለይም ይህ ችግር ባይፈታ ኖሮ ዓለምን እያስደመመ የነበረው ፈጣኑና ተከታታዩ የኢኮኖሚ ዕድገታችን ወደማይመለስበት ወይንም ለመመለስ እጅግ አዳጋች ወደሚሆንበት ደረጃ ማሽቆልቆሉ አይቀርም ነበር፡፡ ምክንያቱም በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት መውደሙን አንረሳውምና ነው፡፡ ፋብሪካዎች እየተቃጠሉ፤ ኢንቨስትመንቶች እየወደሙ፤ የሰው ህይወትም እየጠፋ ለተወሰኑ ወራት ብንቀጥል ኖሮ ኢትዮጵያን አሁን ባለችበት ከፍታ ማሰበ ዘበት ይሆን ነበር፡፡ እያንዳንዳችንም ባለንበት ለመቀጠላችን በህይወትም ለመኖራችን እርግጠኛ መሆን አንችልምም ነበር፡፡

በተለይም ካለፉት በርካታ አስርት ዓመታት የኋልዮሽ ጉዞ በኋላ የደረስንበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የፈጀብንን ረጅም ጉዞ ጠንቅቀን እናውቀዋለን፡፡ እናወቀዋለንናም ተመልሰን ወደዚያ ከፍታ ለመውጣት ጉዞው ቀላል እንደማይሆን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የሆኖው ሆኖ እንደ አገር መከፈል ያለበት ሁሉ ተከፍሎ ሰላማችን ተመልሷል፤ ልማቱም ቀጥሏል፤ እኛም እንዳለን አለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ይህ ከልብ የምለው እውነታ እንጂ ዝም ብሎ ለማለት ያህል ብቻ የሚባል አይደለም፡፡

ለምን?

ምክንያቱ ወዲህ ነው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ አንድም ኢንቨስትመንት አልወደመም፤ አንድም ፋብሪካ አልተቃጠለም፡፡ ይልቁንም አውቀውም ይሁን ሳያወቁ በዚህ እኩይ ተግባር ዙሪያ ሲሳተፉ የነበሩ ግለሰቦች እጃቸውን ለመንግሥት ሰጥተዋል፤ በተቀመጠው የጊዜ ገደብም የጦር መሳሪያ ሳይቀር ዘርፈዋቸው የነበሩ የህዝብና የመንግሥት ንብረቶችን መልሰዋል፡፡ አዋጁ የመለሰልንን ሰላምና ልማት ሳስብ በግሌ አዋጁ ስድስት ወር አይደለም ስድስት ዓመት ቢቀጥል ችግር የለብኝም፡፡

ይህ እውነታ ግን አውቀውም ይሁን ሳያወቁ ለአንዳንድ ወገኖች የሚዋጥ አልሆነም፡፡ አዋጁን አምርሮ የመጥላት ዝንባሌም ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚገለጽ አቋም ከእነዚህ ወገኖች ተመልከቻለሁ፡፡ ይህ ዓይነቱ ተግባር ከታየባቸው አካላት መካከል ነገ አገርን እንመራለን፤ ህዝብን እናስተዳድራለን ከሚሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሆኖ መመልከቴ ትንሽ ነገሩን ከበድ አድርጎብኛል፡፡

ነገሬ ወዲህ ነው፡፡

እንዳልኩዎት አገራችን ገብታበት ከነበረው ቀውስ በኋላ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጨምሮ የተለያዩ ዕርምጃዎችን ወስዷል፤ ለመውሰድም ቃል ገብቷል፡፡ ከብዙው በጥቂቱም የምርጫ ህጉን ለማሻሻል፣ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደርና ለመወያየት፣ በምክር ቤት የሁሉም ወገን ድምፅ የሚሰማበትን ዕድል ለመፍጠር የገባው ቃል ተጠቃሽ ነው፡፡

ይሄንን ቃል ተከትሎም ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የመጀመሪያ ዙር ውይይት አድርጓል፡፡ በዚሁ የመጀመሪያ ውይይትም ፓርቲዎች ድርደሩ ሊካሄድ የሚችልበትን የአሠራር ስርዓትና ድርድሩ እንዴትና በማን መመራት እንዳለበት አለን የሚሉትን አማራጭ ይዘው እንዲቀርቡ ተስማምተው ተለያይተዋል፡፡

የጋናዎቹ የአካን ተረትና ምሳሌም የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፤ «ከእናቷ ያልራቀች ጫጩት የፌንጣ ጭን ታገኛለች»የሚለው፡፡ ለእኔ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የዚህ መንግሥት ወይንም የኢህአዴግ ዘመን ፓርቲዎች ናቸው ብዬ ነው የማምነው፡፡ እውነቱን እናውራም ከተባለ መንግሥት የመሆን ተክለሰውነታቸው ገና ጮርቃ እና በጫጩት ዕድሜ የሚለካ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሆኖም መጠንከርና ማደግ ቢችሉ፤ አገራችንንም በህገ መንግሥቱ ጥላ ስር ሆነው ወደተለየና የተሻለ ደረጃ ማድረስ ቢችሉ (አለባቸው የሚል አመለካከት አለኝ) ማን ይጠላል? ማንም፡፡

ነገር ግን ይህ የሚሆነው ብዙዎቹ ፓርቲዎች እንደሚያስቡት ከትናንት ወዲያ ተመስርተው ዛሬ ላይ አይደለም፡፡ ሰከን ብሎ መጓዝ፤ ቀስ ብሎም መብሰል እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ ይሄ እውነታ ግን በፓርቲዎቹ ዘንድ ብዙም ቅቡል አይደለም፡፡ በእኔ እምነት ፓርቲዎች ሌላ ጫፍ ላይ ቆመው ዘራፍ ማለት ሳይሆን ከኢህአዴግ ጎን ሆነው ከጥንካሬውም ብቻ ሳይሆን ከድክመቱም እየተማሩ መጓዝ ከቻሉና ራሳቸውን ሳያገሉ ማደግ ከቀጠሉ የሚፈልጉትንም ብቻ ሳይሆን ያልጠበቁትንም ጭምር ህዝቡ ይሰጣቸዋል፤ ኢህአዴግም ሊከለክላቸው አይችልም፤ «ከእናቷ ያልራቀች ጫጩት የፌንጣ ጭን ታገኛለች»ማለትም ይሄው ነው፡፡

ከተረትና ምላሴለው በተቃራኒ ባለፉት ሁለት አስርት  የመራራቅ ዓመታት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምን አተረፉ? ምንስ አገኙ? ምንም፡፡ ይልቁንም ትንሽም ቢሆን የነበረቻቸውን የምክር ቤት ወንበር ዜሮ ላይ ነው ያደረሷት፡፡ ስለሆነም መፍትሔው መራራቅ ሳይሆን መቀራረብና አብሮ መሥራት ነው፡፡ የመቀራረቡ ፊሽካ ደግሞ በኢህአዴግ በኩል ተነፍቷል፡፡ ፊሽካውን ሰምተው የመጡ ፓርቲዎች ግን ገና ከወዲሁ ለመስማማት ሳይሆን ላለመስማማት የሚመስል ቅድመ ሁኔታዎቻቸውን እየደረደሩ ናቸው፡፡ 

  ከሳምንት በፊት መኢአድና ሰማያዊ ፓርቲ፤ ከኢህአዴግ ጋር ወደ ሌላ ውይይት ከመግባታቸው በፊት የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ እንደሚጠይቁ መግለጻቸውን አንብቤያለሁ፡፡ ማንኛውንም የህዝብ ጥቅም በድርድሩ አሳልፈው እንደማይሰጡም ተናግረዋል፡፡ ይሄ ጥሩ ነው፡፡ የህዝብን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ፓርቲ መጀመሪያውንም ቢሆን ፓርቲ ሊሆን አይገባውም፡፡ ኢዴፓም በበኩሉ፤ ከምንም አስቀድሞ፣ ላለፉት 25 ዓመታት ኢህአዴግ በተቃዋሚዎች ላይ ሲፈፅም የነበረውን የመብት ጥሰት አምኖ እንዲቀበል እደራደራለሁ ብሏል፡፡

የእኔ ነጥብ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ ለመሆኑ ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት አለመነሳቱ ምን ያገናኘዋል? ይህ አዋጅ እኮ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ገብተንበት ከነበረውና በፍጥነት እየተንደረደርን እየገባንበትም ከነበረው አዘቅት ውስጥ መንጭቆ ያወጣን ነው፡፡ እና ለምን ተብሎ ይህ አዋጅ ለድርድር ይቀርባል? ለመሆኑ ፓርቲዎቹ በዚህ አዋጅ ምን ተጎዱ? ምናልባት ለዚህ ጥያቄ መልሱ አባሎቻችንን እያሳሰረብን ነው የሚል ከሆነ ምላሹ፤ ሰለማዊና ህጋዊ መንገድን ተከትሎ ለመሥራት በተመዘገበ ፓርቲ ውስጥ ሁከት ፈጣሪና ሽብር አንጋች አባል በፓርቲው ውስጥ  ምን ይሠራል? ይሆናል ተከታዩ ጥያቄ፡፡

እኔ እንደሚገባኝ ፓርቲዎች ይህን ለማለት ያህል ያሉት እንጂ በእርግጥ አምነውበት ወይንም የአዋጁ አለማስፈለግ ወለል ብሎ ተገልጦላቸው አይመስለኝም፡፡ ስለተባለ ብቻ ያሉት ሁላ ነው የሚመስለኝ፡፡ ይህ አዋጅ ባይኖር ኖሮ አገሪቷም ባልኖረች፤ እኛም በሌለን እነርሱም ለድርድር ባልተጠሩ ነበር፡፡ ስለዚህ ከዚህ ሁሉ ጀርባ ደጀን የሆነውን አዋጅ ከወዲሁ ለድርድሩ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ምክንያታዊም ተፈጥሯዊም ነው ብዬ አላምንም፡፡

የታሰሩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ይፈቱ የሚለው ቅድመ ሁኔታ ግን በተወሰነ መልኩ ውሃ የሚያነሳ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ወንጀል የፈጸመ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ሁሉ ይፈታ ማለት ስህተትና ራሱም ወንጀል ነው፡፡ ምክንያቱም ማንም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው ካልን ማንም ሰው ወንጀል ሲፈጽም መለካትና መታየት ያለበት በህጉና በፈጸመው ወንጀል እንጂ በተቃዋሚ ድርጅት አባልነቱ ወይንም በፖለቲካ አመለካከቱ ሊሆን አይገባም፡፡ አይደለምም፡፡

ስለሆነም ወንጀል የፈጸመ የአንድ ቅጠል ጠርጋ ቤተሰቧን የምትመራ እናት ልጅም ይሁን የአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ አባል አሊያም የመንግሥት ባለስልጣን ልጅ ወንጀል ከፈጸሙ ሁሉም እኩል ወንጀለኛ ናቸው፡፡ አንዱ ተናጋሪ ስላለው ይፈታ ሌላው ተናጋሪ ስለሌለው ይታሰር ብሎ ነገር አይሠራም፡፡

በዚህ እውነታ ከተስማማን፤ ፓርቲዎች ማለት ያለባቸው «ምንም ወንጀል ያልፈጸሙ፤ በጥርጣሬ ብቻ የታሰሩና ማስረጃ ያልቀረበባቸው አባሎቻችንና አመራሮቻችን ይፈቱ» ነው፡፡ ይሄ ጤናማ አካሄድ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በደፈናው ሁሉም ይፈታ ማለት ነገሩ ሁሉ «የበላችው ያቅራታል በላይ በላዩ ያጎርሳታል» ይሆንብኛል፡፡

በኢህአዴግም በኩል እስከአሁን በተናጠል የሰጠው መግለጫ ባይኖርም ከሰማይ በታች ባሉ ጉዳዮች ሁሉ ለመደራደር ቁርጠኛ መሆኑ በአንድም በሌላም መልኩ ተገልጿል። ጊዜው ሰላማዊ ድርድር የሚካሄድበት፤ በሰለጠነ መንገድም ቁጭ ተብሎ መፍትሔ የሚፈለግበት ነው ካልንና፤ ኢህአዴግም በቀደመው ትውልድ አማካኝነት ለዚህ አሠራር በተከፈለ መስዋዕትነት እዚህ የደረሰ ፓርቲ ነው ከተባለ፤ ቁርጠኝነቱ በእርግጥም ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት መሆኑ የሚታይበት ወቅት አሁን ነው።

በመሆኑም ይህ ድርድር ከዳር ይደርስም ዘንድ ከኢህአዴግ ብዙ ይጠበቃል፤ ድርብ ድርብርብ ኃላፊነትም አለበት። ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንደ አባት ፓርቲ፤ ደግሞም ልምድም እንዳለው በሳል ድርጅት እየመራ ድርድሩን ወደሚፈለገው ደረጃ ማድረስና ታሪካዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል። የአካኖችን «ከእናቷ ያልራቀች ጫጩት የፌንጣ ጭን ታገኛለች» ተረትና ምሳሌም ድርድር ብለው ወደእርሱ በመጡ ፓርቲዎች ዘንድ እውነትነቱን ማሳየት ይገባዋል እላለሁ።

 

አርአያ ጌታቸው

Published in አጀንዳ
Wednesday, 08 February 2017 19:47

አምስት ዓመት ነገ ነው!

 

  አንድ የአበው አባባል አለ፤ «ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለበለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይወረውሩሃል» የሚል። ይህንን አባባል ወደ ፖለቲካው አምጥተን ስናየው ለብዙ ነገሮች ልክ ሆኖ እናገኘዋለን። ፖለቲከኞች ለህዝብ ጥቅም ብለው ፤ በህዝብ ስም ተደራጅተው ፤ የህዝብ በሆነ ነገር ሁሉ እየተጠቀሙ ህዝብን ቢረሱ መልሶ ህዝቡ ያስወግዳቸዋልና አባባሉ እዚህ ላይ ልክ ስለመሆኑ ምንም ክርክር አያስነሳም፤ ጥርጥርም የለውም።

      ከዚህ አንጻር ኢህአዴግን እንደ ድርጅት  መንግሥትንም እንደ መንግሥት ለህዝብ ጥቅም ያላቸውን መሰጠት ስንፈትሽ፤ በተፈጥሯቸው ወይንም በታሪካቸው እንከን የለባቸውም ቢባል ድፍረት አይሆንም። ድፍረት የሚሆነው በዚህ ተፈጥሯቸው በተለይም ኢህአዴግ በበረሃ ዘመን በነበረው የህዝብ አገልጋይነትና ውግንና ልክ አሁንም ድረስ እንዳለ ነው ቢባል ነው።

     ኢህአዴግ በትግል ዘመኑ የነበረው ህዝባዊነትና ቁርጠኝነት  መንግሥት ከመሆኑ በፊት ያስተዳድራቸው በነበሩ ነፃ መሬቶች ላይ የነበሩ ሁሉ የሚያውቁትና የሚመሰክሩት ሀቅ ነው። መንግሥት ከሆነም በኋላ በመጀመሪያዎቹ አምስትና አስር ዓመታት በዝግጅት  ምዕራፍ ላይ ሆኖ እንኳን የነበረው ተቀባይነትና የህዝብ ውግንና ብሎም የአገልጋይነት መንፈሱ ዛሬም ድረስ የሚዘነጋ አይደለም። በተጨባጭም በሀገሪቱ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በማምጣት ታይቷል፡፡

     ይህ ህዝባዊነትና የአገልጋይነት መንፈስ ግን ቀስ በቀስ እየተዳከመ መጥቶና «ጨው ሆይ ለራስህ ስትል ጣፍጥ…» የሚለው አባባልም ተዘንግቶ በድርጅቱ 25 ዓመታት የመንግሥትነት ዘመን ውስጥ ሁለት ጊዜ ተሀድሶ ውስጥ ከቶታል። ለህዝብ ቅሬታ መቀስቀስም አጋልጦታል፡፡

         ኢህአዴግ ከስኬቱም ብቻ ሳይሆን ከውድቀቱም ጭምር የሚማር ፓርቲ መሆኑ ጠቀመው እንጂ፤ በተለይ ባለፈው ዓመት በአገሪቷ ተከስቶ የነበረው የህዝብ ቁጣ ከህዝብ ልብ ውስጥ ፍቆ ሊያወጣው ዋዜማ ላይ ደርሶ ተመልክተናል። ድርጅቱም እንደ ድርጅት መንግሥትም እንደ መንግሥት ህዝብን በማገልገል በኩል ከ10 ዜሮ ማግኘታቸውን አምነው፤ በመልካም አስተዳደር በኩልም መውደቃቸውን በግልጽና በድፍረት ተናዘው ወደ ጥልቅ ተሀድሶ ገብተው ዳግም ጨው ለመሆን አዲስ ነገር ይዘው ብቅ ብለዋል። በተለይም የተፈጠረውን ሞጋች ማህበረሰብና ጥያቄዎቹን በአግባቡ መመለስ ያልቻሉ አመራሮች ከላይ እስከ ታች እንዲነሱ መደረጉ የኢህአዴግ ዳግም ጨው የመሆን ጅማሮ ነው ማለት ይቻላል።

     መንግሥት ጥቅምት 2008 ዓ.ም ያቋቋመውንና ሚዲያዎችም «ተስፋ የተጣለበት ካቢኔ» ብለው የዘመሩለትና ያስዘመሩለትን ካቢኔ በአንድ ዓመት ዕድሜው ያፈረሰውም  ለህዝብ ጥያቄ መልስ መስጠት እንደተሳነው ስላመነ ነው። ይህ ውሳኔም ታች ድረስ ወርዶ የወረዳና ቀበሌ አመራሮች ሳይቀሩ ከህዝብ ወንበር እንዲነሱ ተደርጓል። ይህ የኢህአዴግ «ወደ ነበርንበት ህዝባዊነት እንመለስ» ውሳኔ በእርግጥም የሚያስመሰግን ነው ማለት ይቻላል።

     ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቋቋሙትና አንጻራዊ በሆነ መልኩም ቢሆን በይዘቱ ከእስከዛሬው ካቢኔ  በምሁራን የተዋቀረው አዲሱ  ሥራ አስፈፃሚም እነሆ ሥራውን ከጀመረ 100 ቀናት ተቆጠሩ። በእነዚህ የመጀመሪያ 100 ቀናት ምን ሠራችሁ? የተጣለባችሁን ኃላፊነት እንዴት እየተወጣችሁ ነው? በሚል አዲስ ዘመን አዳዲስ ሚኒስትሮችን አነጋግሯል። ዋነኛ ሥራቸው መረጃ መስጠት የሆኑቱ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች መረጃ መስጠት በሚያቅማሙበትና እንቢተኛ በሚሆኑበት አገር ሚኒስትሮችን በአጭር ቀጠሮ አግኝቶ ማነጋገር መቻል በእርግጥም መንግሥት ጨው የመሆን ጅማሮ ላይ ነው ለማለት ያስደፍራል። ይህም ወደታች ድረስ ሊለመድ ግድ ይላል፡፡

        አዲስ ዘመን ለማነጋገር ጥያቄውን ካቀረበላቸው ሚኒስትሮች አብዛኛዎቹ ጥያቄውን ተቀብለው መረጃውን ሰጥተዋል። ጥቂቶቹ ደግሞ ተባባሪ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ይህ ያለመተባበር ጅማሮ ከወዲሁ መታረምና መወገዝ አለበት። ለዚህ ዘመን አይመጥንምና ሚኒስትሮች ለሚዲያዎች በራቸውን ክፍት ማድረግ አለባቸው። አለበለዚያ ጨው የመሆናቸው ነገር በጊዜ ሂደት ማክተሙ አይቀርም።

        ሚኒስትሮቹ በ100 ቀናት ውስጥ አበረታች ሥራዎችን ሠርተዋል። መጪው ጊዜ የሥራ መሆኑንም አምነው ወደ ሥራው ባህር ገብተዋል። በእርግጥ ጥሩ ዋናተኛ ካልሆኑ ሰምጠው መቅረታቸው እርግጥ ነው። ምክንያቱም የተቀመጡበት ወንበር የሚፋጅ፣ ዕለት ከዕለትም አዳዲስ የልማት ጥያቄዎችን የሚያነሳ ህዝብ ባለቤት የሆነበት ነውና። ስለሆነም ሳይታክቱ መሥራትና ብዙሃኑን ማሰለፍ  የግድ መሆኑን ሊረዱ ይገባል።

       አምስት ዓመት ነገ ነው። ምንም ሳይሠራ በቃላት ጨዋታ ብቻ ተሸንግሎ የምርጫ ፈተና የሚታለፍበት ጊዜ አክትሟል። አመርቂ ሥራ ካልተሠራና ህዝቡን ማርካት ካልተቻለም አምስት ዓመት ድረስ መቆየት እንደማይቻል ህዝብ አሳይቷል፤ ከፈረሰው ካቢኔም  በግልጽ መረዳት ይቻላል። መንግሥትም ይሄንን አምኖ ተቀብሏል።

      ስለሆነም ሚኒስትሮች ሆይ የመጣችሁት ከምትሄዱት ያነሰ፤ የምትሄዱትም ከመጣችሁት የሚበልጥ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በውል ተረድታችሁ የህዝቡን የልብ ትርታ እያዳመጣችሁ መልስ መስጠት እንዳለባችሁ አትዘንጉ። ሲሠሩ የሚያመሰግን ሳይሠሩም ቸኩሎ የማያማርር አስተዋይና ምክንያታዊ ህዝብ ስለምታገለግሉ ኩራት ሊሰማችሁ ይገባል። ኩራታችሁ እራታችሁ ይሆን ዘንድም የተሰጣችሁን የህዝብ ወንበር ለህዝብ ጥቅም ፣ ለፍትህና  ለእኩልነት ብቻ አውሉት፤ ይሄንን ማድረግ ሲቻልም ጭምር ነው «ታላቅ ነበርን ታላቅ እንሆናለን» የሚለውን ብሂል እውን ማድረግ የሚቻለው።

Published in ርዕሰ አንቀፅ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የቀረቡለትን ዘጠኝ የተለያዩ አዋጆች አፀደቀ። ሰባቱ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራትና ተቋማት ጋር ያደረገቻቸው የብድር ስምምነት አዋጆች ናቸው።

ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ጉባዔውን ትናንት ያካሄደው ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ጨምሮ ሰባት የብድር ስምምነቶችንና የመንግሥት ባለስልጣናት ከስልጣን ሲወርዱ ሊያገኟቸው የሚገቡ መብቶችና ጥቅሞችን የተመለከተውን አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

ምክር ቤቱ ቅድሚያ ያጸደቀው የኢትዮጵያ ወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድን ለማቋቋም የቀረበለትን አዋጅ ሲሆን፤ ተዘዋዋሪ ፈንዱ የሚቋቋመው ከኢፌዴሪ መንግሥት በሚመደብ አስር ቢሊዮን ብር መሆኑንና፤ በዋነኛነትም ወጣቶች ያላቸውን አቅም ለሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲያውሉ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አለማየው ጉጆ አብራርተዋል።

ለጅማ ₋ጭዳ እና ሶዶ ₋ሳውላ የመንገድ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውለውንና በኢትዮጵያ መንግሥትና በአፍሪካ ልማት ፈንድ መካከል የተደረገውን የ25 ሚሊዮን አምስት መቶ 89 ሺ ስምንት መቶ 66 ብር አዋጅም ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

 በተመሳሳይም፤ መንግሥት ከነዳጅ አምራችና ላኪ አገራት ፈንድ ለዓለም አቀፍ ልማት ጋር ለሀሙሲት-እስቴ የመንገድ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ 20 ሚሊዮን ዶላር፤ እንዲሁም  ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር የተደረገውንና ለመቀሌ-ዳሎል እና ሰመራ-አፍዴራ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውለውን 104 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት አጽድቋል።

 ለአሳታፊ አነስተኛ የመስኖ ልማት ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚውለውንና ከዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ጋር የተደረገው የ103 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ብድር ስምምነትም ፓርላማው በሙሉ ድምጽ ተቀብሎ አጽድቆታል።

ለገናሌ ዳዋ 3 ይርጋለም 2 ሶዶ 2 ሃዋሳ 2 የኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የሚውለውንና  ከቻይና ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ  ጋር የተደረገውን የ249 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነትም አጽድቋል።

   በተመሳሳይም፤ ምክርቤቱ በኢፌዴሪ መንግሥትና በቻይናው ኤክስፖርት ኢምፖርት  ባንክ መካከል ለገርቢ ግድብና ማሰራጫ መስመር እንዲሁም ለመጠጥ ውሃ ማዘጋጃ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውለውን፤ እንዲሁም ለአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል ማስፈጸሚያ  የሚውለውን የብድር ስምምነቶች መርምሮ አጽድቋል። 

 በመጨረሻ ምክር ቤቱ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባሎችና ዳኞች ከኃላፊነት የተነሱ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና መሪዎች የሚያገኙዋቸውን መብቶችና ጥቅሞችን ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በዝርዝር ተመልክቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

 

ዳንኤል ዘነበ

Published in የሀገር ውስጥ
  • ሌሎች ኃላፊዎችም እንዲጠየቁ አፈ ጉባዔው ተጠይቀዋል

 

ከመድሃኒት ግዥና ንብረት አስተዳደር ጋር በተያያዘ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በዋና ኦዲተርና በህዝብ ከፍተኛ ቅሬታ ሲቀርብበት የነበረው የመድሃኒት ግዥና ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ስራቸውን በፍቃዳቸው መልቀቃቸው ተገለጸ። የመንግስት ወጪና አስተዳደር  ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥፋት ያለባቸው የኤጀንሲው ሃላፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ለአፈጉባዔው ደብዳቤ መጻፉን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተናግረዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሀነ ለአዲስ ዘመን ብቻ እንደገለጹት፤ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መስቀሌ ሌራ ስራቸውን በራሳቸው ፈቃድ ለቀዋል። በምትካቸውም ሰው ለማስቀመጥም ኮሚቴ ተቋቁሞ 16 ሰዎችን በማወዳደር የመጨረሻው ሰው ተለይቶ ውሳኔው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርቧል።

ሚኒስቴሩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረባቸው ግለሰብም ተቀባይነት ማግኘታቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር ይፍሩ፤ የዳይሬክተሩ ሹመት በተያዘው ሳምንት ይፋ እንደሚደረግና ስራም እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪና አስተዳደር  ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥፋት ያለባቸው የኤጀንሲው ኃላፊዎች በሙሉ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለአፈጉባዔው ደብዳቤ መጻፉን አስታውቋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ለአዲስ ዘመን እንደገለጹትም፤  እርሳቸው የሚመሩት ቋሚ ኮሚቴና የማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በጋራ በመሆን ባደረጉት ማጣራት፤ የኤጀንሲው የመንግስት ሀብት አያያዝና አሰራር ለሙስና የተጋለጠ መሆኑን አረጋግጠዋል። በመሆኑም አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ ሲባልም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የኤጀንሲው እና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ኃላፊዎች በተገኙበት ችግሮቹ ተገምግመው ትክክለኛ ስለመሆናቸው መግባባት ላይ መደረሱን አመልክተዋል።

እንደ አምባሳደር መስፍን ማብራሪያም፤ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ኤጀንሲው በተለዩት ችግሮች ላይ የህግ ጥሰት የፈጸሙ ኃላፊዎችና ሌሎች አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ፤ ችግሮቹንም ጊዜው በሚጠይቀው መንገድ እንዲፈቱና የህብረተሰቡን ችግር የሚፈታ የመዋቅር ማሻሻያና አሰራርም እንዲዘረጋ ቋሚ ኮሚቴዎቹ  አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

ዋናው ኦዲተር በኤጀንሲው ላይ ባከናወናቸውና በደረሰባቸው የተለያዩ የኦዲት ግኝቶቹ ላይ በመመርኮዝም መወሰድ ያለበት እርምጃ እንዲወሰድ የመጨረሻ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ለምክር ቤቱ አፈጉባዔ ከ15 ቀናት በፊት ደብዳቤ መጻፉቸውን ያስታወሱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ አፈጉባዔውም ለጠቅላይ ሚኒስቴሩ ያለውን ችግር እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብረሃነ በኤጀንሲው ችግሮች ዙሪያ ለምክር ቤቱ ቀርበው ምላሽ መስጠታቸውን ያነሱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ ሚኒስትሩ በምላሻቸው ኤጀንሲው ከፍተኛ ችግር ያለበት መሆኑንና በአገሪቱ መድሃኒት በሚፈለገው ደረጃ እንደማይቀርብ፣ በተለይም የመንግስት ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች መድሃኒት በአግባቡ እንደማይደርሳቸው፣ በእቅድ የተመሰረተ ግዥ እንደሌለ፣ ወደ አገር ውስጥ መግባት የሌለባቸው መድሃኒቶች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውና በጊዜ መወገድ ያለባቸው እንደማይወገዱ ማመናቸውን ተናግረዋል።

  የፌዴራል ዋና ኦዲተር ከ2005 እስከ 2007 ዓ.ም ብቻ በመድኃኒት ግዥና ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ ዋና መስሪያ ቤትና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መጋዘኖች ውስጥ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ሳያልፍ ለጤና ተቋማት መሰራጨት የነበረባቸው ነገር ግን ያልተሰራጩ 569 ሚሊዮን 833 ሺ 919 ብር ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶች፣ የህክምና መሳሪያዎች መገኘታቸውን ሪፖርት ማቅረቡ አይዘነጋም።

በታህሣሥ 2009 ዓ.ም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኤጀንሲውን የኦዲት ሪፖርት ባዳመጠበት ወቅት፤  ኤጀንሲው በውስጥ ጨረታ፣ በቀጥታ ግዥና በዋጋ ማቅረቢያ በድምሩ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ግዥ መፈጸሙን፤ ነገር ግን የግዥው ሂደትና አጠቃላይ ሁኔታ ግልጽ እንዳልሆነ ተገልጿል።

ኤጀንሲው የግዥ አፈጻጸም መስፈርትን ሳያዘጋጅ የ16 ሚሊዮን 863 ሺ 333 ብር ግዥ መፈጸሙንም ዋናው ኦዲተር በሪፖርቱ አቅርቧል። ከዚህም በተጨማሪ ከ105 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎችን ኤጀንሲው ማቅረብ ሲገባው አለማቅረቡን መገለጹንና ይህንኑም በተከታታይ ዘገባ ማቅረባችን የሚታወስ ነው፡፡

 

አጎናፍር ገዛኽኝ

Published in የሀገር ውስጥ

መንግሥት በየደረጃው ለተፈጠሩ የህዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ መልስ መስጠት ላይ የነበረበትን ስንፈት በግልጽ አምኖ ከለየ በኋላ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም ተቋቁሞ የነበረውን ካቢኔያቸውን ጥቅምት 22 ቀን 2009 አፍርሰው በምትኩ አዲስ ካቢኔ ማቋቋማቸው ይታወሳል። የአዲሱ ካቢኔ አባላት በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርበው ቃለ መሀላ ከፈጸሙና ሥራ ከጀመሩ 100 ቀናትን አስቆጠሩ። ለመሆኑ አዳዲሶቹ ሚኒስትሮች ጠብቀው የገቡበት ሥራና መሬት ላይ ያለው እውነታን እንዴት አገኙት? በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት ምን ሰሩ፤ ምንስ አቅደዋል?

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፤ ጽህፈት ቤቱ ከተሰጠው ተልዕኮ አንጻር በሰው ኃይልና በአደረጃጀት ጠንካራ እንደሚሆን አስበው ቢገቡም ተቋሙን እንደጠበቁት አለማግኘታቸውን ገልጸዋል። በጽህፈት ቤቱና በሌሎች ተቋማት መካከል ያለው ግንኙነትም የላላና የአሰራር ክፍተት ያለበት፤ የሰው ኃይሉም ሆነ መዋቅሩ ተፈትሾ መስተካከል እንዳለበት መረዳታቸውን ተናግረዋል።

ዶክተር ነገሪ ባለፉት 100 ቀናት ከኮሙኒኬሽንና ከመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች ጋር ውይይትና ግምገማ በማድረግ በዘርፉ በአጭርና በረጅም ጊዜ የሚሰሩትን መለየታቸውን ይናገራሉ። በአጭር ጊዜ የሚሰሩትን መከወን መጀመራቸውንና በረጅም ጊዜ የሚሰሩት ደግሞ ጥናት ስለሚያስፈልጋቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መተማመን ላይ ተደርሶ የማስተካከያ ጥናት ማስጀመራቸውን ነው የገለጹት።

«በቀጣይም የኮሙኒኬሽንና መገናኛ ብዙሃን በአገር ውስጥ ገለልተኛና ተዓማኒ ሆነው የተጀመረውን የዴሞክራሲ፣ የሰላምና የአገር ግንባታ ሥራዎችን በማገዝ፣ የተሸፈኑ ችግሮችንም ርቃናቸውን በማስቀረት፤ በውጭው ዓለምም መገናኛ ብዙሃኖቻችን የኢትዮጵያና የአፍሪካ ድምጽ እንዲሆኑ ለማድረግ በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ይቀጥላሉ። የኮሙኒኬሽን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገምግመው ጥሩ አፈጻጸም ያላቸው እንዲቀጥሉ፤ የአቅም ችግር ያለባቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ተጨማሪ ትምህርት ይሰጣቸዋል» ብለዋል ዶክተር ነገሪ።

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ ዶክተር እያሱ አብርሃ፤ ቀደም ሲልም በዘርፉ የሰሩ ቢሆንም ኃላፊነቱን አክብደው ጠብቀውት እንደነበርና ወደ ሥራ ሲገቡ የተለየ ነገር እንዳልገጠማቸው ያመለክታሉ። ዶክተር እያሱ እንደገለጹትም፤ ባለፉት 100 ቀናት ከአጠቃላይ አመራሮች ጋራ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ምንነት ዙሪያ በመግባባት የአስተሳሰብ አንድነት ለመፍጠር ሰርተዋል። በዋናነትም የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ በሥነ ምግብ ደህንነት፣ በመስኖ ሥራ፣ በግብርና ኤክስፖርት፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በግብርና መካናይዜሽን፣ ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በመተካት፣ አሲዳማና ጨዋማ  አፈርን በማከም፣ በአፈር ለምነት ጥናት፣ የአየር ንብረት መዛባትን በመቋቋም እና በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና አሰራር ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋራ የተለያዩ ሥራዎች ተከናውነዋል። በቀጣይም በስፋት ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እያደረጉ ናቸው።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ በበኩላቸው፤ «መጀመሪያ ከጠበቅኩት ብዙም የተለየ ነገር አላገኘሁም። በህክምናው ዘርፍ የሚካሄዱ ግንባታዎች ግን ከጠበኩት በላይ ከፍተኛ ሆኖብኛል» ብለዋል። እንደ ፕሮፌሰር ይፍሩ ገለጻም፤ ባለፉት 100 ቀናት በእቅድ ዘመኑ ተግባራዊ የሚሆነውን የጤና እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ተንቀሳቅሰዋል። ድንገተኛ ወረርሽኞች ሳይስፋፉ ለመቆጣጠር የሚያስችል ኢንስቲትዩት የማቋቋም፣ የህክምና መሳሪያ ለማሟላት፣ የመድኃኒት ግዥና ፈንድ አገልግሎት ኤጀንሲን የማስተካከል፣ በሆስፒታሎች ያለውን ኋላ ቀርና ረጅም ሰንሰለት የማስቀረት፣ በአራት ዓመት ውስጥ አምስት ሺ ስፔሻሊስቶችን የማስተማር ዝግጅት፣ ከውጭ የሚገቡም ሆነ በአገር ውስጥ የሚመረቱ መሳሪያዎች ወጥ የሆነ ደረጃ እንዲኖራቸው ፖሊሲ የመቅረጽ፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእራሱ የቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጣቢያ እንዲኖረው፣ የመረጃ አርካይቭና ባዮ ባንኪንግ የማቋቋምና ሌሎች መሰል ሥራዎችን አከናውነዋል። በቀጣይም የተጀመሩ ሥራዎችንና ሌሎችን አጠናክሮ ለመቀጠል አቅደዋል። 

የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትሩ ዶክተር ገመዶ ዳሌ፤ የተመደቡበት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በፊት ሲሰሩበት ከነበረበት ሙያ የሚያያዝ በመሆኑ የሥራ አካባቢ ከመቀየር ውጪ ሁሉንም እንደጠበቁት ማግኘታቸውን ይናገራሉ። በ100 ቀናት ውስጥም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና በሥሩ ያሉት ሦስቱ ተጠሪ ተቋማት ተናበውና ተጋግዘው እንዲሰሩ ለማድረግ ከጠቅላላ ሠራተኛውና ከተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር የጋራ መግባባት ፈጥረዋል።

«የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስተካከል ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን ወስደናል። የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ዓላማ ለማሳካትም ግምገማ አድርገን አጠናቀናል። ከግንባታ ጋር ተያይዞ የነበሩ የተዘበራረቁ አካሄዶችን አስተካክለናል፤ ሁለት ዓለም አቀፍ መድረኮችን የመምራትና የኢትዮጵያና የአፍሪካን ድምጽም በማንጸባረቅም አበረታች ሥራዎችን ሰርተናል» ሲሉ ተናግረዋል። የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በሚፈለገው ደረጃ ኃላፊነታቸውን አለመወጣት፣ የአካባቢ ጥበቃ መጓደል እና ተናቦ የመስራት  ችግሮች ባለፉት 100 ቀናት ፈተና እንደሆኑባቸውም ሚኒስትሩ አልሸሸጉም።

የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ደግሞ፤ ስለመስሪያ ቤቱ በተወሰነ ደረጃ የሚያውቁ ቢሆንም ከገቡ በኋላ ሰፊ ሥራዎችን እንደሚሰራ መረዳታቸውን ይገልፃሉ። ኃላፊነቱን ከተረከቡ በኋላም የመጀመሪያ ሥራቸው እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን ግምገማ  አድርገዋል። በተለይም ከሁለተኛው የዕድገትና ተራንስፎርሜሽን እቅድ አንፃር ምን ያህል እንደተሰራና ባለድርሻ አካላት ጋር የመተዋወቅ ሥራ እንደሰሩ አንስተዋል።

ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ እንደተናገሩትም፤ በ100 ቀናት ውስጥ ሰፋፊ ችግር ያለባቸውን ፕሮጀክቶች የመስክ ጉብኝት በማድረግ መፍትሄዎችን አስቀምጠዋል፤ ተጓተዋል የተባሉትን ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች በአዲስ መልክ እንዲካሄዱ አድርገዋል፤ የፕሮጀክቶችን ቀረጻ አስጀምረዋል፤ ከክልሎች ጋር እየተሰሩ ያሉትን ሥራዎች በመገምገም እንዲፋጠኑ አድርገዋል። የመጠጥ ውሃ፣ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋፋት የዝግጅት ሥራ ሰርተዋል፣ ሠራተኛውን በአመለካከት ለመቀየር በጥልቅ ተሃድሶ ማሳለፍና ሌሎች መደበኛ ሥራዎች አከናውነዋል።

ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀጣይም፤ የአገሪቷን አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት ኤሌክትሪክን ተደራሽ አድርጎ ተጠቃሚን ማርካት፣ የውሃና ፍሳሽ አቅርቦትና አወጋገድን ማሳደግ፣ መስኖን በማስፋፋት ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንዳቀዱ አመልክተዋል።

የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በበኩላቸው፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከተቋቋመ ገና አንድ ዓመት መሆኑን አንስተው፤ የአዲስነት ችግር ቢኖሩበትም  «ያገኘሁት  የጠበቅሁትን ነው» ብለዋል።   እሳቸው እንዳሉትም ኃላፊነቱን እንደተረከቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ስለተቋሙ አሰራርና አደረጃጀት መማር ማወቅ ነበር። እዚህ ላይ በመመስረትም ያለፈውን ሥራ በመገምገም በቀጣይ የሚሰሩ ሥራዎችን የማቀድና አደረጃጀቱንም የማስተካከል ሥራ መስራታቸውን አንስተዋል። ከስድስት ወር የሥራ አፈጻጸም ጋር በማቀናጀት የሠራተኛው የተሃድሶ ግምገማ እንዲያካሂድ በማድረግ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ አምጥተዋል። በቀጣይ የተከለሰውን እቅድ በእንስሳትና ዓሣ ሀብት ዘሪያ ከተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር በማድረግ በቀጣይ ተፈፃሚነቱን ለማረጋገጥ ርብርብ ለማድረግ እየተዘጋጁ ናቸው።

በዘርፉ ትልቁ ችግር የሆነውን የኳራንታይን ሥራዎችን አጠናቆ ወደ ሥራ የማስገባት፣ ህገ ወጥ ኮንትሮባንዶችን ለመቆጣጠር ህዝባዊ ንቅናቄ የመፍጠር እና ሌሎች መደበኛ ሥራዎችን ለማከናወን ማቀዳቸውን የተናገሩት ያለፉት 100 ቀናት ውጤታማ መሆናቸውን በመግለጽ ነው።

 የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ  ዶክተር  ኢንጂነር  ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው፤  ባለፉት 100 ቀናት  በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና በዘጠኙ ተጠሪ ተቋሞች ከማኔጅመንት አባላትና ከሁሉም ሠራተኞች ጋር ውይይት በማድረግ ለችግሮች መፍትሄ ማስቀመጥ፤  በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የዕቅድ ክለሳ በማድረግ፣ በሁለቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ሦስተኛ ዲግሪ ለማስጀመር መርሀ ግብር በመንደፍና ከተለያዩ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የማስተሳሰር ሥራ በመስራት አሳልፈዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻም፤ የአገሪቱን የ10 ዓመታት የቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታ ከልሰዋል። በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተስማሚነት ምዘና ቤተ ሙከራዎች እንዲመሰረቱ አድርገዋል። በሁሉም ክልል እና  መስተዳድሮች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲዎች እንዲጠናከሩና የኢኖቬሽን ሥርዓቱ ተጠናክሮ የሚሄድበትን መንገድ ፈጥረዋል። በሁሉም ክልሎች ውስጥ ያሉት ኤጀንሲዎችን ማጠናከርና የአቅም ግንባታ እና ሌሎች ሥራዎችን ማከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም የተቋሙ ራዕይና ተልዕኮዎችን የማሳካት፣ ተቋሙን ከልማዳዊ አሰራር የማላቀቅ፣ የተጀማመሩት የትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክቶችን የማሳካት በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከላት ያልተናበበና የተበጣጠሰ ምርምር በማስቀረት በፍኖተ ካርታው መሰረት እንዲካሄድ ማስቻል፣ የኢትዮጵያን ሳተላይቶችን ህዋ ላይ ማስቀመጥ፣ አዋጭነት ያላቸው ቴክኖሎጂዎች ዕውን ማድረግና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተስጥዖ ያላቸውን የወደፊቱ ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶችን ማፍለቅ ትልቁ ሥራቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

ዜና ሐተታ

አጎናፍር ገዛኸኝ

               

Published in የሀገር ውስጥ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።