Items filtered by date: Thursday, 09 February 2017

አቶ ልደቱ አያሌው፤                                                     ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፤                                 አቶ ዝናቡ ይርጋ፤

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በህጋዊነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ 62 አገር አቀፍና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ፣ የኢትዮጵያ ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር (ኢፍዲኃግ) እና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ በግንባርነት የተዋቀሩ ፓርቲዎች ናቸው፡፡

አንዳንድ የፖለቲካ ምሁራን በተለይም ኢህአዴግን ‹‹ግንባር ሆኖ መደራጀቱ ህብረብሄራዊነቱን አሳጥቶታል» የሚል ሃሳብ ይሰነዝራሉ፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ ከዚህ በመነሳትም ‹‹ኢህአዴግ ወደ ውህደት መምጣት አለበት›› ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

የፖለቲካ ምሁሩ አቶ ልደቱ አያሌው፤ ራሳቸውን በብሄር ማንነት ያደራጁ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመደራጀት እንደምክንያት የሚያነሱት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዋናው የፖለቲካ ችግር የብሄር ብሄረሰብ የማንነት ጥያቄ ነው የሚል እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም ችግሮችን ለመፍታትም በብሄር ብሄረሰብ ተደራጅቶ መታገልን ቀዳሚ ምርጫቸው አድርገዋል፡፡ ይህንን አስተሳሰብ የሚደግፉ ሃይሎች አደረጃጀታቸውም ሆነ አሰራራቸው በዋናነት የብሄር ቅኝት ላይ ያጠነጠነ መሆኑ ህብረብሄራዊነትን እንዳሳጣው ይናገራሉ፡፡

 ‹‹የብሄረሰብ ጥያቄ በአንድ ወቅት አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ በአገራችን እንደምናየው ይሄ መንግስት አሸናፊ ሆኖ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ በህገመንግስት ደረጃ መልስ ከመስጠት አልፎ ክልሎች የራሳቸውን አካባቢ በራሳቸው ከማስተዳደርም በላይ  እስከመገንጠልም ድረስ መብት እንደተሰጣቸው ይጠቅሳሉ፡፡ ይሄ ጥያቄ ከተመለሰ በኋላ ግን  የፓርቲዎች አደረጃጀት አሁንም ብሄረሰባዊ ማንነት ላይ መሰረት አድርጎ ቀጥሏል›› የሚሉት አቶ ልደቱ፤ አንድ ችግር በአንድ ወቅት ከተፈታ በኋላ ሌሎች ችግሮችን መፍታት ሲፈለግ  አደረጃጀትንም በዚያው መጠን ማጣጣም እንደሚገባ ይጠቅሳሉ፡፡

የፖለቲካና ማህበራዊ ችግሮችን በጣምራ መፍታት የሚቻለው ህብረ ብሄራዊ የሆነ አመለካከትን መሰረት ያደረገ አደረጃጀት መፍጠር ሲቻል እንደሆነ የሚያምኑት አቶ ልደቱ፤ በአገሪቱ አንድ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር ከተፈለገ ኢህአዴግ ከግንባርነት ወደ ውህደት ሊመጣ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡

እንደ እርሳቸው እምነት፤ የብሄር አደረጃጀት በርካታ ውስንነቶች አሉበት፡፡ መነሻው ራሱ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ዋናው የፖለቲካ ጥያቄ ‹‹የብሄር ጥያቄ ነው›› የሚል ነው፡፡ ሌሎቹን ጥያቄዎች ደግሞ በቀጣይነት ያያቸዋል፡፡ ይሁንና የአገሪቱ ህዝቦች ከማንነት ጥያቄ ባለፈ  የዴሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የሰላምና የአንድነት ጥያቄያቸው አይሎ ነው የሚታየው፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች  በተጨባጭ መመለስ የሚቻለው የፓርቲው አደረጃጀት ከግንባር ወደ ውህደት ሲመጣ ብቻ ነው፡፡

ኢህአዴግ ከግንባርነት ወደ ውህደት ከመጣ የብሄረሰብና የማንነት ጥያቄ ዳግም ሊያገረሽ አይችልም ወይ? ለሚለው ስጋት፤ አቶ ልደቱ «የብሄር ጥያቄ የኢትዮጵያ አንድ ጥያቄ ነው ብሎ ማመንና ያለችግር እንዲፈታ መታገል የሚቻለው በብሄር ስለተደራጁ ብቻ ነው ብሎ ማሰብ በራሱ ስህተት ነው» ይላሉ፡፡ ኢዴፓን አብነት አድርገውም «የኛም ፓርቲ የማንነት ጥያቄ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ብሎ ያምናል፡፡ ችግሩ እንዲፈታም በፅናት ይታገላል፡፡ ይህንን ለማለት ግን በብሄረሰብ መደራጀት አላስፈለገንም» ይላሉ፡፡ በመሆኑም በህብረብ ሄራዊነት ወይም አስተሳሰብን መሰረት አድርገው የሚደራጁ ፓርቲዎች ለብሔር ብሄረሰቦች መብት አይቆረቆሩም ብሎ ማሰብ የተሳሳተ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡

እንደ አቶ ልደቱ እምነት፤ በአገሪቱ እየተፈጠሩ ላሉት ችግሮች ዋናው መነሻ የገዢው ፓርቲ አደረጃጀት ነው፡፡ ከውስጣዊ አደረጃጀቱ ባለፈ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ህብረተሰቡ ከአካባቢ ጉዳዮች ባለፈ በጋራ እጣፈንታው እንዳያስብ አድርጎታል፡፡ ዜጎች ከጋራ ጉዳዮቻቸው ይልቅ በልዩነቶቻቸው ላይ እንዲያተኩሩም አድርጓል፡፡ ህዝባዊ ህብረብሄራዊነት እየተመናመነ ሄዶ ግለኝነት ወይም ማንነት ልቆ ወጥቶ ለግጭቶች መንስኤ ሆኗል፡፡ ይሄ ሁኔታ በሂደት አገሪቱ ለአመታት ስትመራባቸው በነበሩት መደበኛ ህጎች መተዳደር አቅቷት ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል፡፡ አሁንም ቢሆን በየአካባቢው የሚነሳውን ጥያቄ በሃይል ከማፈን ባለፈ በፍቅርና በሰላም ለመፍታት አልተቻለም፡፡ በተጨማሪም ሰዎች በእውቀታቸውና በልምዳቸው ሳይሆን በብሄረሰባዊ ማንነታቸው የሚሾሙበት ሁኔታ በመፈጠሩም የአገሪቱ አንድነት ላይ «የእኔ ድርሻ የቱ ነው?» የሚል ቀመር ውስጥ እንዲገባ እንዳደረገ ያምናሉ፡፡

የህግ ባለሙያው አቶ ዝናቡ ይርጋ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ‹‹የኢህአዴግ ግንባር መሆን አሁን ለተፈጠሩት ችግሮች መንስኤ ሆኗል›› የሚለው አስተሳሰብ ችግሮችን አለአግባብ ከማጋነን የመጣ መሆኑ ነው፡፡ ድርጅቱ ግንባርም ሆነ ወደ ውህደት ቢመጣ ችግሮቹ እንዳይከሰቱ አያግዳቸውም፡፡ ሁለቱም አደረጃጀቶች የየራሳቸው ችግሮች ይኖሯቸዋል፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ያሉት አራት  ድርጅቶች ምንም እንኳ የየራሳቸው ልዕልና እና ህልውና ይዘው ፓርቲውን ቢያቋቁሙም በተግባር ግን የውህደት ባህሪ አላቸው፡፡ ከኢህአዴግ ተጨባጭ ሁኔታም የሚወጡ ፖሊሲዎችን ሁሉም ድርጅቶች  የሚያስፈፅሙ መሆኑ  ከስያሜ ለውጥ ባለፈ አጠቃላይ አሰራሩ ለውህደት የቀረበ አድርጎታል፡፡

 «ድርጅቱ ሁሉንም ብሄረሰቦች በእኩል መንገድ የሚያሳትፍ መሆኑ ጠቃሚ ነው፤ ነገር ግን ስያሜው በራሱ ልዩነቶች እንዲበራከቱና አንድነትም እንዲጠፋ አድርጓል ብዬ አላምንም» ይላሉ፡፡ ከዚህ ይልቅም ለማንነት ጥያቄዎችና ለግጭቶች መበራከት ዋና ምክንያት የሆነው የፌደራሊዝም ስርዓት ፅንሰ ሀሳብ የተተገበረበት አግባብ ነው፡፡ ህገመንግስቱ ለሁሉም ህዝቦች በቋንቋቸው እንዲናገሩ መብት ቢሰጥም የክልሎች አወቃቀር ግን ነባራዊ እውነታን ያላገናዘበ በመሆኑ የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን አግልሏል፤ በማያውቁት ቋንቋም  እንዲጠቁሙ አስገድ ዷቸዋል የሚል ሃሳብ ይሰነዝራሉ፡፡

   «ብሄርተኝነት እንዲስፋፋና ልዩነቶች እንዲበራከቱ ያደረጉት የተጠቀሱት ሁኔታዎች ናቸው» የሚሉት አቶ ዝናቡ፤ ወደ ውህደት ቢመጣም የፌደራሊዝም አወቃቀሩ እስካልተ ስተካከለ ድረስ የማንነት ጥያቄዎች መነሳታቸው እንደማይቀር ያምናሉ፡፡ «አሁንም ቢሆን የሚዋሃዱት ፓርቲዎች እንጂ ክልሎች አይደሉም፤ ስለዚህ አንድነቱን የፓርቲው ስያሜ መቀየር አያመጣውም» የሚል መከራከሪያ አላቸው፡፡

   አቶ ልደቱ በበኩላቸው፤ ገዢው ፓርት በአንድ በኩል አንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ የመፍጠር ፍላጎት አለኝ ቢልም በሌላ በኩል ግን አደረጃጀቱና ይህንን ተከትለው የመጡ ህጎችና አጠቃላይ ድንጋጌዎች ከዚህ አስተሳሰብ ተፃራሪ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ኢህአዴግ አደረጃጀቱን ሊገመግም ይገባል፡፡ በብሄረሰባዊ አደረጃጀት ይልቅ ወደ አስተሳሰባዊና ህብረብሄራዊ ድርጅትነት መቀየር ወሳኝነት ላይ ያሰምሩበታል፡፡

 በኢህአዴግ ምክር ቤት  ጽህፈት ቤት የፓርቲ ጥናት ምርምርና ርዕዮተ ዓለም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ፓርቲውን የመሰረቱት አባል ድርጅቶች በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ አቋም አላቸው። የፓርቲው አደረጃጀት በአገሪቱ በነበረው የብሄር ብሄረሰቦች ጥያቄ መነሻነት  ከነባራዊ ሁኔታ የተቀዳ በመሆኑ ረጅም ርቀት ለመጓዝ አስችሎታል። አደረጃጀት ነባራዊውን ሁኔታ የሚሸከም መሆኑ ግምት ውስጥ መግባት አለበት።

  «አደረጃጀቱ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲሰፍን መሰረት ጥሏል። የአገራችንን የድህነት ገፅታ ለመቀየር ያስቻለ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት አንዲፈጠር አድርጓል» የሚሉት ሃላፊዋ፤ የአደረጃጀቱ መገምገሚያ ውጤት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ምንም እንኳን በህገመንግስቱ  የብሄር ብሔረሰብ ጥያቄ ቢመለስም የቀድሞው አድሏዊ አገዛዝ አመለካከቶች ሙሉ በሙሉ እንዳልከሰሙ በመጠቆም፤ «ቁም ነገሩ ለህብረተሰቡ ለውጥ ማምጣት የሚችል አደረጃጀት መሆኑ ላይ ነው» ይላሉ፡፡

  «የማንነት ጥያቄ ማሳረጊያው የሕዝቦችን የመልማት አቅምና እድል ማውጣት መቻል ነው።  ስለዚህ ብሔር ብሔረሰቦች ያዋቀሯቸው ክልሎች ያላቸውን የመልማት እድል ተጠቅመዋል። ይህ በአካባቢ ጉዳይ ብቻ የማተኮርና  በሰፈር የመታጠር ጉዳይ አይደለም» ይላሉ፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱም ህብረተሰቡ በአካባቢያዊ ጉዳዮች እንዲታጠር አድርጓል የሚለው ከነባራዊ ሁኔታውም ጋር እንደማይሄድ ይጠቅሳሉ። ይሄን ለመሸርሸር የሚያንዣብቡ አመለካከቶችና ድርጊቶች አሉ።  እነርሱ ላይ መስራት ይገባል ባይ ናቸው፡፡

  እንደ አቶ ልደቱ እምነት፤ በኢህአዴግ ውስጥ ያሉት አራቱ ፓርቲዎች ህብረብሄራዊ በሆነ መልኩ ቢጣመሩ የድርጅቱን ውስጣዊ ጥንካሬ ያጎለብተዋል፡፡ ይህም በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ የማንነትና የጥቅም ግጭቶች እልባት እንዲገኝ እገዛ ያደርጋል፡፡ ይህ መሆን ካልቻለ ግን  አሁን አራቱ ድርጅቶች ወደ  ግጭት ሊያመሩ ይችላሉ፡፡ ይህም የህዝብ ለህዝብ ሽኩቻ እንዲበራከትና የአገሪቱም አንድነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል።

  ወይዘሮ ሙፈሪያት በበኩላቸው፤  ኢህአዴግ ሃሳብ የሚያንሸራሽር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት እንደመሆኑ በተለያዩ ወቅቶች በሚኖሩ መድረኮች ሁሉ ወደ ውህደት የመምጣቱ ጉዳይ መነሳቱንና  ሀሳቡ እያደገ መጥቶ በድርጅቱ የተለያዩ ጉባኤዎች መንፀባረቁን ይጠቅሳሉ።  ግልፅ የሆነ አቅጣጫ  እንዲቀመጥለት መደረጉንና በጥናት እንዲመለስ መወሰኑን ያመለክታሉ፡፡ ለዚህም የቤት ስራ የተሰጠው የጥናትና ምርምር ክፍል ተቋቁሞ ጉዳዩን እንዲመለከተው ተወስኗል።

 

ዜና ትንታኔ

ማህሌት አብዱል

Published in የሀገር ውስጥ

 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየአካባቢው የሚከፈቱ የስፖርት ማዘውተሪያ ቤቶች እየተበራከቱ መጥተዋል። የማዘውተሪያዎቹን መስፋፋት ተከትሎ በርካታ ወጣቶች የሰውነታቸውን ቅርፅ ስፖርታዊ ቁመና ለማላበስ ሲጥሩ ይስተዋላል። የሰውነት ቅርፅ ለማሳመር የሚረዱ ማሽኖችንም ለማግኘት የሚኖራቸውም ጥቅም የማይናቅ ነው። ሆኖም በስፖርት ቤቶቹ የሚሰሩት የስፖርት አይነቶች ምን ያህል ሳይንሱን በጠበቀ መልኩ ይከናወናሉ የሚለውን መጠየቅ ወሳኝ ነው።  ከዚያ ባሻገር የእነዚህ ስፖርት ቤቶች ፍቃድ አሰጣጥና ክትትል ምን ይመስላል የሚለውን መቃኘት ይገባል።

ወጣት ናትናኤል ወርቅነህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ በአካባቢው ወደሚገኝ ስፖርት ቤት መሄድ ያዘውራል። እርሱ በሚሰራበት ስፖርት ቤት ብዛት ያላቸው ሰዎች ይጠቀማሉ። በሰው ብዛት በሚፈጠር የአየር እጥረት የተነሳ በማዘውተሪያው ውስጥ ደስ የማይል ሽታ እንደሚፈጠር ይናገራል። እንዲሁም የስፖርት አሰራሩን የሚያማክር ባለሙያ የለም። ባለሙያ ባለመኖሩ በየግርግዳው የተለጠፉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚሳያዩ ምስሎችን በመመልከት ይሰራል።

በስፖርት ቤት ውስጥ ለመገልገል የሚጠየቀው የሚሰራበትን ክፍያ እንጂ የጤና እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ላይ ክትትል እንደማይደረግም ይገልጻል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከስፖርት በኋላ የገላ መታጠቢያና አጠቃላይ ንፅህናም የተሟላ እንዳልሆነም ይናገራል። ከሚሰራው ስፖርት ጋር ተመጣጣኝና ተገቢ የሆነ የአመጋገብ ሂደት የሚያማክር ባለሙያም የለም። በየአካባቢው የሚገኙ አብዛኞቹ የስፖርት ቤቶችም ተመሳሳይ ችግር እንደሚኖርባቸው መገመት አያዳግትም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ በቂ ክትትል የሚፈልግ ነው፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ማህበራት ማደራጃ ፍቃድና ቁጥጥር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አቡሽ ደግፌ፤ ቢሮው ከዚህ ቀደም የስፖርት ቤቶችን የመቆጣጠር ሃላፊነት እነዳልነበረው ያስረዳሉ። ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የጂምናዚየሞች፣ ማህበራትና የስፖርት ንግድ ቤቶችን የመቆጣጠር፣ ፍቃድ የመስጠት እና የማደስ ክፍል በማቋቋም ስራ እንደጀመረ ያስታውሳሉ። ስራውን በማህበራት ማደራጃ፣ ቁጥጥር እና ክትትል በመክፈል የጂምናዚየሞችን ደረጃ የማውጣት ስራን ይሰራል።

ለስፖርት ቤቶች (ጂምናዚየም) ፍቃድ ለመስጠት የሚቀመጡ መስፈርቶች እንዳሉ ይናገራሉ። መስፈርቶቹ ጂምናዚየሞቹ ሊያሟሏቸው የሚገቡ የንፅህና መስፈርቶች፣ የስፖርት ባለሙያ፣ የመፀዳጃ ቤትና ገላ መታጠቢያ፣ የመጀመሪያ እርዳታ ማሟላት ይጠበቅባቸዋል። ስፖርት ቤቶቹ ለተገልጋዩ ምቹ እንዲሆኑ በቂ አየርና ብርሃን ማስገባትና የተስተካከለ ከመሆን አንፃርም በአግባቡ ማሟላት ይገባቸዋል። እኚህን ሁሉ አሟልተው ሲገኙ በመተዳደሪያና ማቋቋሚያ ደንብ መሰረት ፍቃዱ ይሰጣቸዋል። ከአንድ አመት በኋላ የጂምናዚየም ባለቤት ፍቃዱን ለማሳደስ ሲመጣ ባለሙያዎች ወደ ቦታው በመሄድ መስፈርቶቹ መሟላታቸውን ቢሮው ያረጋግጣል።

ነገር ግን አቶ አቡሽ እንደሚሉት ቁጥጥሩ መጀመሪያ ላይ እንጂ ሁሉንም የሚያዳርስ አይደለም። በመሆኑም የስፖርት ቤቶቹን ብቃትና ስራቸውን በመቆጣጠሩ ረገድ በስፋት ያልተኬደበት እንደሆነም ይገልፃሉ። ለዚህም እንደምክንያት የሚያነሱት ነገር አለ፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት የስራው ሃላፊነት ለቢሮው ከተሰጠ ገና አጭር ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የባለሙያ እጥረት ነው። ከዚህ ባሻገር ቁጥጥርና ክትትል ለማካሄድም በከተማው የሚገኙትን መሰል ስፖርት ማዘውተሪያ ቤቶች በቁጥር እንደማይታወቁ ለመረዳት ተችሏል። በዚህ አመት የተቀመጡትን መስፈርቶች ያላሟሉ አራት የስፖርት ቤቶችና አንድ የስፖርት ንግድ ቤት ፈቃዳቸው ተሰርዟል። መስፈርቱን አሟልተው ሲገኙ ፍቃዳቸው እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል።

ከሚጠየቁት መስፈርት በተጨማሪ በስፖርት ቤቶቹ የሚዘወተሩት ስፖርቶች አይነትና መጠን ሳይንሱን የጠበቀ ነው? የተጠቃሚውንስ ጤና ከመጠበቅ አንፃር የሚደረግ ክትትል አለ? ለሚሉት ጥቄዎች፤ አቶ አቡሽ ምላሽ አላቸው፡፡ እንደርሳቸው ማብራሪያ በስፖርት ቤቶቹ የሚሰራው ስፖርት በሁለት የተከፈለ ነው። የመጀመሪያው በተጠቃሚው አካል ብቃት ላይ ተመስርቶ ያለ ምንም ተጨማሪ መሳሪያ በሙዚቃ በመታጀብ ብቻ የሚሰራ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ስፖርቱን በማሽን በመታገዝ ወይም የስፖርት ማሽኖችን በመጠቀም የሚሰራ ነው።

በዚህ መሰረት ወደ ስፖርት ቤቶቹ የሚመጣ ማንኛውም ተገልጋይ በመጀመሪያ የስፖርተኛውን አካላዊ ሁኔታ የሚገልፅ የህክምና ማስረጃ ማምጣት ይተበቅበታል። እንዲሁም ‹‹ስፖርቱን የሚሰራው ለተለየ ምክንያት ከሆነ ለየትኛው የህመም ምን አይነት ስፖርት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚሰራ የሚገልፅ የሀኪም ማስረጃ ይዞ መምጣት አለበት›› ይላሉ። በዚህ መሰረት ስፖርት የሚሰራው ሰው ቁመት፣ ክብደት እንዲሁም አጠቃላይ የጤንነት ሁኔታ ያማከለ ስፖርት ነው መስራት ያለበት። በስፖርት ቤት የሚሰሩት ስፖርቶች ለጤና እና የአካል ብቃትን ለማሻሻል ነው። ነገር ግን እነኚህን ሁሉ መስፈርቶች ለማሟላት በመቆጣጠር ላይ ክፍተት እንዳለ ይናገራሉ።

ደረጃቸው ከፍ ያሉ ሆቴሎች ውስጥ የሚገኙ ጂምናዚየሞች ማሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በየአካባቢው የሚገኙ የስፖርት ቤቶች ክፍተት መኖሩን ይገልጻሉ። ከህብረተሰቡ ከሚደርሳቸው ጥቆማ በመነሳት በቢሮው እንደ እቅድ በመያዝ እነኚህን ስፖርት ቤቶች የመቆጣጠር ስራ ይሰራሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ወንድሙ ታደሰ፤ ስፖርት ለህብረተሰቡ ጤና ጠቃሚ፣ በስራውም ጠንካራና ንቁ ማህበረሰብ ለመፍጠር ትልቅ ድርሻ እንዳለው ያስረዳሉ። የህብረተሰቡን ጤና መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠውና ሁሉም በአቅሙ ስፖርት በመስራት ራሱን ጤናማና ጠንካራ ማድረግ እንደሚችል ይናገራሉ።   ለዚህ ደግሞ በየአካባቢው የሚገኙ የስፖርት ቤቶች ስፖርትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ከማድግ አኳያ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ነው። ነገር ግን እነኚህ ስፖርት ቤቶች የስፖርትን ጠቀሜታ እንደሚያጎሉ ሁሉ ጉዳትም ሊያስከትሉ እንደሚችሉ መታወቅ አለበት።

በየሰፈሩ የሚገኙ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ ቤቶች ውስጥ ምን እንደሚሰራ፣ ማን መስራት እንዳለበት፣ እንዴት ነው የሚሰራው? የሚሉትን ጥያቄዎች በአግባቡ ማንሳት አስፈላጊ እንደሚሆን ያስረዳሉ። በተለያየ እድሜ ክልል ያሉና በተለያየ የጤና ሁኔታ ያላቸው ዜጎች ስፖርት ይሰራሉ። ስለዚህ የተለያየ የእድሜ፣ የአካል እና የጤና ደረጃ ያላቸውን ህብረተሰቦች እንደየልዩነታቸው የሚሆን ስፖርት መስራት አለባቸው። ማንኛውም ሰው ስፖርት ለመስራት ወደ አካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ ቤቶች ሲሄድ በቅድሚያ የኪሎ፣ የቁመትና የጤና ሁኔታውን የሚገልፅ የሀኪም ማስረጃ ሊኖረው ይገባል። ስፖርቱንም የሚሰራው በሀኪም ታዞለት ከሆነ የህመሙን ሁኔታ፣ መስራት ያለበትን የስፖርት አይነት፣ ለምን ያህል ጊዜና እንዴት መስራት እንዳለበት የሚገልፅ መሆን አለበት ይላሉ።

እንደዚህ አይነት አሰራር ከንድፈ ሃሳብ በበለጠ ሊሰራበት ይገባል። ለስፖርት ቤቶቹ ፍቃድ ከመስጠትም ባሻገር እንዴት ነው የሚሰሩት የሚለውንም መቆጣጠር አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻሉ። ሳይንሱን በጠበቀ መልኩ መስራት ያስፈለገበት ምክንያት ወደ ስፖርት ቤቶቹ የሚመጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ጤናን ለመጠበቅ፣ የሰውነት ቅርፅን ለመጠበቅ፣ የሰውነት አቅምን ለማጎልበትና ሌሎችም ምክንያቶች ስለሚሆን መጀመሪያ መለየት ስላለበት ነው።

እንደ መምህሩ ገለፃ በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው ስፖርት ቤት የሚታዩት እንቅስቃሴዎች ከገንዘብ ማግኘት ጋር የተያያዘ ስለሆነ በመዘናጋት ጤንነትን የሚጎዱ ነገሮች እንዳይፈጠር ቁጥጥር ያስፈልጋል። ስፖርት የጥቅሙን ያህል ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ መሰረት ካልተሰራ ጉዳቱ የዚያኑ ያህል የከፋ ይሆናል። ሁሉም ሰው ጤናውን ለመጠበቅ አንድ አይነት ስፖርት መስራት አይጠበቅበትም። በስፖርት ቤቶች ውስጥ በብዛት የሚሰራው የክብደት ማንሳት ነው። ነገር ግን ሁሉም ስፖርት ቤት የሚሄድ ሰው አንድ አይነት ስፖርትን ብቻ የሚሰራ ከሆነ ከአላማ ጋር የማይጣጣም ይሆናል። የህብረተሰቡን ጤና ከመጠበቅ አኳያ የከተማው ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ለስፖርት ቤቶች ፈቃድ ከመስጠትም በላይ እንዴት እንደሚሰራ በአግባቡ ቢቆጣጠር የህብረተሰቡን ጤና በአግባቡ ለመጠበቅ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ይመክራሉ።

 

ሰላማዊት ንጉሴ

Published in ስፖርት

አሶሼትድ ፕሬስ ዕለታዊውን ዘ ቻርሎቴ ኦብዘርቨር እማኝ አድርጎ ከስፔን ዜናውን ሲያሰራጭ ‹‹ገንዘቤ ክብረወሰን መስበሩን ዓመታዊ ልማዷ አድርጋዋለች›› በማለት ነበር፡፡ የዜና ምንጩ ይሄን ለማለት የተገደደው አትሌቷ በየዓመቱ አዳዲስ የዓለም ክብረወሰኖችን መሰባበሩን በዚህም ዓመት መግቢያ ገፍታ መቀጠሏን ተከትሎ ነው፡፡ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ከትናንት በስትያ ምሽት በስፔን የካታሎን ግዛት ሳባዴል ከተማ በተካሄደ የ2000 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር አዲስ የዓለም ክብረወሰን እስመዝግባለች፡፡

ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ) ውጤቱን በድረገፁ እንዳሰፈረው፤ ገንዘቤ የሰበረችው አዲስ ክብረወሰን እ.አ.አ 1998 ሮማኒያዊቷ ገብሬላ ዛቦ በጀርመን ሲንዲልፊን ከተማ የተያዘ ነበር፡፡ 2000 ሜትር ውድድሩን ለማጠናቀቅም 5 ደቂቃ 23 ሰኮንድ ከ75 ማይክሮ ሰኮንድ ፈጅቶባታል፡፡ ይሄም ገብሬላ ዛቦ ውድድሯን ካጠናቀቀችበት ሰዓት በሰባት ሰኮንዶች የተሻለ መሆኑ ታውቋል፡፡

ማህበሩ እንደገለጸው ይሄ ውጤት እ.አ.አ 1994 በስኮትላንድ ኤድምብራ በተካሄደ ከቤት ውጪ ውድድር በአየርላንዳዊቷ ሶኒያ ሱሊቫን በ5 ደቂቃ 25 ሰኮንድ 36 ማይክሮ ሰኮንድ የተያዘውን ክብረወሰን የሚመለከት አይደለም፡፡

የ25 ዓመቷ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ እ.አ.አ 2015 ያሻሻለቻቸውን 1500 ሜትር (ሁለት ጊዜ) እንዲሁም 5000 ሜትር ጨምሮ በአንድ ማይል፣ በሁለት ማይልና በ3000 ሜትር ውድድሮች ፈጣን ሰዓት የግሏ ማድረግ ችላለች፡፡ ከውድድሩ በኋላ ‹‹ክብረወሰን መስበሬ በጣም አስደስቶኛል፤ በቀጣይ የተሻሉ የውድድር ሰዓቶችን ማስመዝገብ እንደምችል ይሰማኛል›› ያለችው ገንዘቤ፤ በውድድሩ ወቅት በስቴዲየሙ የነበረው ከፍተኛ ቅዝቃዜ እንዳስቸገራትም አልሸሸገችም፡፡

አትሌቷ ባለፉት አራት ዓመታት በተለይም በቤት ውስጥ ውድድሮች የዓለም ክብረወሰኖችን በመሰብሰብ ፉክክሯ ከአትሌቶች ይልቅ ከሰዓት ጋር ሆኗል። ከሁለት ዓመት በፊት በሁለት ሳምንት ውስጥ ሦስት የዓለም ክብረወሰኖችን የግሏ በማድረግ የዓለምን ትኩረት መግዛት ችላለች፡፡ አትሌቷ ከዓመት በፊት በሞናኮ ዳይመንድ ሊግ የ1500 ሜትር የዓለም ክብረወሰን በማሻሻል ከቤት ውጪ በሚካሄዱ ውድድሮችም ትልቅ አቅም እንዳላት አሳይታለች። ከሞናኮው ድሏ ማግስት በተካሄደው የቤጂንግ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናም ለኢትዮጵያ በታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የወርቅ ሜዳሊያ በርቀቱ ማስመዝገብ ችላለች። በዚህም በዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የዓመቱ ኮከብ አትሌት ሽልማት አሸንፋለች።

ገንዘቤ በተጠቀሱት ዓመታት ከመካከለኛ እስከ ረጅም ርቀቶች ስኬታማ ጉዞን ብታደርግም ያሳለፍነው የውድድር ዓመት ካለፉት አኳያ ጥሩ የሚባል አልነበረም። በተለያዩ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች የተለመደውን ክብረወሰን ታስመዘግባለች ተብሎ ቢጠበቅም አውራ ጣቷ ላይ በደረሰባት ጉዳት ምክንያት ከውድድሮች ለመራቅ ተገዳለች። ይህም በሪዮ ኦሊምፒክ በታሪክ የመጀመሪያ ሊሆን የሚችል የወርቅ ሜዳሊያ በ1500 ሜትር እንዳታስመዘግብ እንቅፋት ሆኖባት አልፏል። ገንዘቤ በሪዮ ኦሊምፒክ በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ባታስመዘግብም ያጠለቀችው የብር ሜዳሊያም ቢሆን በመድረኩ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል።

 

ብሩክ በርሄ

Published in ስፖርት
Thursday, 09 February 2017 19:16

ከጎዳናዎቹ መካከል

የአዲስ አበባ ጎዳናዎች የተለያዩ ትዕይንቶችን ያስተናግዳሉ። የትዝብቴ መነሻ ከሆኑት መካከል በአንዱ በርካታ ተሽከርካሪዎችን በሚያስተናግደው ጎዳና ከተመለከትኩትና ቀልቤን ከሳበው ጉዳይ ልጀምር።   አስፓልቱ ጥሩምባቸውን አጉልተው በሚያሰሙ ብዙ ተሽከርካሪዎች ታጭቋል፡፡ ጥቂቶቹ ወደ ላይ፣ ጥቂቶቹ ወደታች፣ ቀሪዎቹ ወደ ጎን ግራና ቀኝ ለመሄድ አፍንጫቸውን ቀስረው «እኔ ልቅደም እኔ ልቅደም» በሚል አንዱ በሌላው መንገድ ተሰነቃቅረዋል፡፡

 በእኔ ልቅደም ራስ ወዳድ ብልጠት የተሰበጣጠሩት አሽከርካሪዎች ግን እርስ በእርስ ከመፋጠጥ በቀር ምንም አይነት የመከባበርና የመተባበር መንፈስ አይነበብባቸውም፡፡ መፋጠጥ ብቻ፡፡ ‹‹ና ወንድሜ፤ እኔ ወደ ኋላ መለስ ልበልልህና አንተ እለፍ›› የምትለዋ ትህትና የለችም፡፡ ብትኖር ደግሞ እሱ ሲስገበገብ በገባበት ቀዳዳ ሌላ የእርሱ ቢጤ ዘዋሪ ተከትሎ መርፌ በመካከሉ ማስገባት እስከሚያቅት ድረስ ከኋላው መጥቶ ሰፍቶታል፡፡

ይህ እንግዲህ በብዙ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች የምናስተውለው ተከባብሮ ያለመንዳት ወይም ያለመተላለፍ  ኢ-ስነምግባር ውጤት መሆኑ ነው፡፡ ድንቅ፤ ድንቅንቅ የሚለኝ ደግሞ እነዚህ በግዴለሽነትና በራስ ወዳድነት የሚሽቀዳደሙትና ለእግረኛ ቅድሚያ መስጠት የሹፍርና ውድቀት የሚመስላቸው ዘዋሪዎች የትራፊክ ፖሊስ መለዮ ሲመለከቱ የሚያሳዩት የተቀደሰ ስነምግባር ነው፡፡ በዚህች አጋጣሚ ሁሉም ህግ አክባሪና ጥንቁቅ ሾፌሮች መስለው ለመታየት ይሞክራሉ፡፡

ከደቂቃዎች በፊት በእድሜ የገፉ እግረኛ መንገድ ሲያቋርጡ ‹‹ከእርሶ ህይወት ወይም ክብር የእኔ የጥጋብ ችግር ይበልጣልና ዞር በሉልኝ›› የሚል እስኪመስል ድረስ የመኪናውን ጡሩምባ እያስጮኸ ሲያስደነብር የነበረ አሽከርካሪ ቀይ የትራፊክ መብራት አስቁሞት ራቅ ብሎ ደግሞ የትራፊክ ፖሊስ ኮፍያ ሲያይ የሚያሳየው ትህትና ያስቃል- ያስገርማልም፡፡ አረንጓዴው የእለፍ መብራት በርቶ እንኳ ትራፊክ ፖሊሱን እያየ ‹‹ጋሼ ልለፍ ወይስ መብራቱ ተበላሽቶ ይሆን?›› እያለ ፈቃድ የሚጠይቅ ይመስል ይሽቆጠቆጣል፡፡ አንዳንዱ ዘዋሪ እንዲያውም ትራፊክ ፖሊሱን እያየ ‹‹እርስዎ እዚህ ጠራራ ጸሀይ ላይ ከሚቆሙ እኔ ሙሉ ወጪውን ሸፍኜ መብራቱን ላሰራው›› ብሎ የሚማጸንም ይመስላል፡፡

 የትራፊክ ፖሊስ ካላዩ በጨዋ ደንብ መንዳት ማንን ገደለ? መከባበር የሚሉት ኢትዮጵያዊ ስነ ምግባር ምን ጅብ በላው? እዚህ ጋ ይህን አይነቱ መጥፎ ስነምግባር ያላቸው የመኖራቸውን ያህል ግብረ ገብ፣ ህግ አክባሪና ለወገን ህይወት ተቆርቋሪ አሽከርካሪዎች መኖራቸውን እንዳልዘነጋሁ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

በዚያው ልክ ደግሞ ለገዛ ህይወታቸው ያን ያህል ክብር የሌላቸው እግረኞችም አሉ፡፡ ከሚሮጥ ተሸከርካሪ ጋር እንደ አህያ እየተጋፉ መንገድ የሚያቋርጡ ሞልተዋል፡፡ የእግረኛ ማቋረጫ ድልድይ አፍንጫቸው አጠገብ ተዘርግቶ በአደገኛ ሁኔታ የመንገድ ማካፈያ ብረቶችና የሲሚንቶ አጥሮች ላይ እየተንደባለሉ የሚሻገሩትን አገር ይቁጠራቸው፡፡

በአውራ ጎዳናዎቻችን የሚንከላወሱት በሀሳብ የሚናውዙ እግረኞችም ያሳዝኑኛል፡፡ አንድ ቀን ግን ያጋጠመኝ አስቂኝም አሳዛኝም ነገር ነው፡፡ አንድ ወጣት ግለሰብ አስፓልት ማቋረጥ ሲጀምር አንዲት አማላይ፣ ጭኖቿን በአጭር ቀሚስ ያጋለጠች ኮረዳ ከእርሱ በተቃራኒ ስትመጣ ያያል፡፡ አይኖቹ ከጭኖቿ እንደተተከሉ ባጠገቡ ታለፋለች፡፡ ያው ከፊት ለፊት ያደነቀውን ውበት ከኋላም ለማጣጣም አንገቱን አጠማዞ አይኖቹን እዚያው ጭን ላይ ተክሎ መንገዱን ማቋረጥ ቀጠለ፡፡

ድንገት ግን የመኪና ጡሩምባና የፍሬን ዘግናኝ ሲጥሲጥታ ጆሮው ላይ ሕብረት ፈጥረው ከሄደበት የምኞት አለም ቀሰቀሱት፡፡ ዞር ሲል በዕድሜ ጠና ያለ ሾፌር በመኪናው መስኮት አንገቱን አስግጎ ‹‹ምነው ልጄ? በቀልብህ ሁን እንጂ!›› ይለዋል፡፡ ወጣቱም ቀበል አድርጎ ‹‹ይቅርታ ጋሼ፤ ትንሽ ሀሳብ ገብቶኝ ነው›› ይልና መኪናውን አልፎ መንገዱን አቋርጦ ይሄዳል፡፡ ሾፌሩ ግን መኪናውን እያስነሳና ጭንቅላቱን ግራ ቀኝ እየወዘወዘ ‹‹አይይ… ይሄ የኑሮ ውድነት እኮ ወጣቱን ሁሉ ናላውን አዞረው፤ ይገርማል›› ብሎ ጉዞውን ቀጠለ፡፡

 

ሄኖክ ጥበቡ

Published in መዝናኛ
Thursday, 09 February 2017 19:13

የቀን መቁጠሪያዬ

እመኑኝ የኔ ቀን መቁጠሪያ እንደማንኛውም ሰው ጠረጴዛ ወይም ግድግዳ ላይ የተሰቀለ  አይደለም(በርግጥ ሌላም ሰው የኔ ዓይነት ቀን መቁጠሪያ ይኖረው ይሆናል)፡፡ እናላችሁ የኔ ቀን መቁጠሪያ የወረቀት ሳይሆን የሰው ነው፡፡ ጥር፣ የካቲት ወይም 1፣2፣3 እያልኩ ወረቀት ላይ መፈለግ ሳይሆን በቀጥታ ‹‹ዛሬ ቀን…. ነው›› የሚል ሰው አለኝ፡፡

እንግዲህ የቀን መቁጠሪያዬ ያልኳችሁ አከራዬ ናቸው፡፡ የቤት ኪራይ የምክፍለው ወር በገባ በሃያ ሰባተኛው ቀን  ነው፡፡ እኔም ይህንን ቀን የመረጥኩት ያለምክንያት እንዳይመስላችሁ(ተነቃቅተናል አይደል?) ያው እንግዲህ የደመወዝ ሰሞን ስለሆነ ነው፡፡ ሃያ ሰባት መቼ እንደሆነ የማውቀው በ25 ወይም በ26 አካባቢ አይደለም፡፡ አከራዬ ቶሎ ቶሎ እየመጡ ‹‹ዛሬ ቀኑ እንዲህ ነው›› ይሉኛል፡፡ ለምሳል በ19 ይመጡና ‹‹ዛሬ ገብርኤል ነው አይደል?›› ይሉኛል፡፡ «አዎ ምነው የጽዋ ማህበር አለብዎት እንዴ? ስላቸው ‹‹ ኧረ አይደለም ዛሬ ገብርኤል ከሆነ የነገ ሳምንት መድሃኒያለም ነው ብዬ ነው እንጂ›› ይህን የሚሉኝ የመድሃኒያለም ማህበርም ኖሯቸው ሳይሆን ብር የምሰጣቸው በ27 ስለሆነ ነው፡፡

አንድ ቀን ደግሞ በ24 መጡና እንዲህ አሉኝ ‹‹ዛሬ ተክልዬ ናቸው አይደል?›› ሲሉኝ ነገሩ ስለገባኝ ቶሎ ብዬ «አዎ ተክልዬ ናቸው፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ደግሞ መድሃኒያለም ነው» አልኳቸው፡፡ ቀኑን ማስታወሴ ገርሟቸው ‹‹እንዴ! አንተም 27ን በጉጉት ነው እንዴ የምትጠብቀው?›› አሉኝ፡፡ « አይ! ‹ማዘር› (እናት ከምላቸው ማዘር ስላችው ደስ ይላቸዋል) ሃያ ሰባትን እኮ እርስዎ ብቻ ሳይሆኑ እኔም በየዕለቱ ነው የማስታውሰው» አልኳቸው፡፡ ‹‹አንተ ደግሞ ምኑ ነው ያጓጓህ?›› አሉኝ፡፡ እርስዎ ብር ለማግኘት በጉጉት ይጠብቁታል፣ እኔ ደግሞ ብር ስለማወጣ በስጋት እጠብቀዋለሁ፡፡ ስለዚህ 27 ለሁለታችንም የማይረሳ ቀን ነው አልኳቸው፡፡

አከራዬ የሚያገለግሉኝ እንደ ቀን መቁጠሪያ ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ በአንዳንድ ወቅታዊ ዜናዎች ላይ ከፌስቡክ ቀድመው ያልተጣራ ወሬም ቢሆን ሹክ ይሉኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በጣም የሚያናድዱኝ ግን ይሄ ‹‹እንኳን ደስ ያለህ›› ብለው የሚጀምሩት ነገር ነው፡፡ አንድ ዕለት እንዲህ ሆነላችሁ፡፡ ቤተሰቦቼ የቤት ውስጥ አስቤዛ እንልክልሃለን ብለውኝ ነበር፡፡ ቤት ካጣችሁኝ እንኳን ለአከራዬ ስጡልኝ ብዬ ነበር፡፡ ይህን በጉጉት እየጠበቅኩ ሳለሁ አንድ ቀን ገና ብቅ ስል ሲያዩኝ ‹‹እንኳን ደስ ያለህ!›› አሉኝ፡፡ እኔም በጉጉት ሰፍ ብዬ «እንኳን አብሮ ደስ አለን ! ምን ተገኘ?» አልኳቸው፡፡ ‹‹ዛሬ በተለብጂን ለመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ እንደተጨመረ ሰምቻለሁ›› ሲሉኝ ምን ለማለት እንደፈለጉ ስለገባኝ ዝም አልኩ(ታዲያ ምን ይጠበስ ነበር ማለት)፡፡

 ይህን ከመናገራቸው አስከትለው ደግሞ ወደ ገበያና ንግድ ገቡ፡፡ ‹‹ምን አንተ ደግሞ ከቤት በሚገኝ ኪራይ እኮ መኖር አልቻልንም፡፡ እያንዳንዱ ነገር ተወደደ፡፡ አሁን እንግዲህ የቤት ኪራይ ልጨምርብህ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ነገር በተወደደበት ዘመን መኖር አልቻልኩም›› አሉኝ፡፡ «ታዲያ የኑሮ ውድነት በቤት አከራዮች ላይ ብቻ ነው እንዴ? በተከራዮች ላይም እኮ ነው» አልኳቸው ይውጣልኝ ብዬ እንጂ እንደማይሰሙኝ እያወቅኩ፡፡ ‹‹በል አሁን እዚህ ተቀምጨ ስጠብቅህ የቆየሁ ይሄን ልንገርህ ብዬ ነው፡፡ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ኪራይ ትጨምራለህ?›› ብለውኝ ብድግ ሲሉ አላስችልህ አለኝና «ይስሙኝማ ‹ማዘር› ደመወዝ መጨመሩን እኮ እኔም እንደ እርስዎ በቴሌቪዥን ነው የሰማሁ፡፡ ገና ደመወዙ ሳይጨመር እርስዎ ቀድመው ጨመሩ፡፡ ታዲያ ከየት አምጥቼ ልሰጥዎት ነው? አይ! ካሉ ደግሞ ቤቱን እለቅልዎታለሁ» አልኳቸው፡፡ ‹‹ካልጨመርክ ቤቱን ትለቃለህ፣እንዲያውም ዛሬ መንገዱ ሁሉ ቤት ፈላጊ ነበር›› አሉኝ(ሁሌም ማስፈራሪያቸው ይቺ ናት)፡፡

አከራዬ በኔ ላይ የሚሰሩትን ግፍ ሳይ ከኔ ይልቅ ለእርሳቸው አዝናለሁ፡፡ አንዳንድ ቀን ካመሸሁ ሰው ይዤ የምገባ እየመሰላቸው በር በሩን እንዳዩ ያመሻሉ፡፡ ድንገት እንኳን የጎረቤት ሰው በዚያ ካለፈ ‹‹ማነው?›› ይላሉ፡፡ እንዲያውም መጸዳጃ ቤት እንኳን ስንት ጊዜ እንደሄድኩ የሚቆጥሩት ይመስለኛል፡፡ አንድ ቀን ማን እንደሆነ ሳያረጋግጡ ወደ መጸዳጃ ቤቱ ሰው ሲገባ አዩ(እኔ ነበርኩ)፡፡ ማን እንደሆነ ለማገራረጥ አስበው መሰለኝ በሩ አካባቢ ሆነው‹‹ሰው አለ?›› አሉ፡፡ እኔም ሁኔታቸው ገርሞኝ ከውስጥ ሆኜ «የለም» አልኳቸው(መቼም ሰው ባይኖር ኖሮ እንዲህ የሚል አይኖርም ነበር)፡፡ እርሳቸውም በመገረም ‹‹ደግሞ ከውስጥ ሆኖ ሰው የለም ይለኛል እንዴ! ሆ!ሆ! ሆ! ጉድ እኮ ነው እናንተው!›› እያሉ ወደ ቤት ገቡ፡፡

ሌላው የሚያሳዝኑኝ ነገር ደግሞ የኔን ቤት እንደራሳቸው ቤት አለማየታቸው ነው(ከኪራዩ በስተቀር)፡፡  አንድን ያገለገለ ዕቃ ‹‹ልጣለው ወይስ የሚያስፈልግበት ጊዜ ይኖር ይሆን?›› ብለው ከተጠራጠሩ የሚያስቀምጡት እኔ ካለሁበት ቤት አጠገብ ነው(መጋዘን አደረጉኝ እኮ)፡፡

ስለ አከራዬ ያሳቀቺኝን የአንድ ቀን ገጠመኝ ልንገራችሁና ለቀቅ ላድርጋቸው (ወረድኩባቸው እኮ)፡፡ ልብስ አጥበው አስጥተዋል፡፡ እኔም ውሃ እንደመጣች ነው ልብስ ማጠብ  ብዬ ለቅለቅ አደረኩት፡፡ የልብስ ማስጫውን ለመጠቀም «የደረቀ የደረቀውን ላንሳው?» ስላቸው ‹‹አይሆንም እንዳትነካው›› ብለው ከለከሉኝ፡፡ እኔም ውሃው እየተንጠፈጠፈ ቤት ውስጥ ሰቀልኩት፡፡ የእርሳቸው ልብስ በጣም ደርቆ ስለነበር ነፋስ እያወረደ ስናጥብበት የነበረበት ስፍራ ላይ ከሚገኘው ጭቃ ላይ ጥሎታል (እንዴት አንጄቴን እንዳሻረኝ)፡፡

 

ዋለልኝ አየለ

Published in መዝናኛ

የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573 /2000 «ግንባር» ማለት ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተናጠል ህጋዊ ህልውናቸው እንደተጠበቀ  የጋራ ስያሜ፣ የፖለቲካ ፕሮግራም እና መተዳደሪያ ደንብ ኖሯቸው ለመንቀሳቀስ ሲወስኑ የሚደራጅ አካል መሆኑን ያትታል። «ውህደት» ማለት ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ በህግ መሠረት ተመዝግበው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ ላይ ተዋህደው አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ የሚመሰርቱበት ሁኔታ እንደሆነ ያስረዳል።

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞከራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ)  ደርግን  ለማስወገድ በተደረገው የትጥቅ ትግል በተሳተፉ ፓርቲዎች በ1981ዓ.ም የመሰረቱት ድርጅት  ሲሆን፤ ከምስረታው ጀምሮ «ግንባር» የሚለውን አደረጃጀት ይዞ ዘልቋል።   ብሄር ብሄረሰቦችን የሚወክሉ ፓርቲዎችን መሰረቱ ያደረገው ኢህአዴግ አደረጃጀቱ በአገሪቱ የነበረውን ነባራዊ ሁኔታና ችግር መነሻ በማድረግ እንደተዋቀረ ቢጠቀስም፤ እጥረት አለበት ውህደትም መፍትሄው ነው የሚሉ ተደጋጋሚ አስተያቶች ይሰነዘርበታል።  በኢህአዴግ ምክር ቤት  ጽህፈት ቤት የፓርቲ ጥናት ምርምርና ርዕዮተ ዓለም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ የሆኑት ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ከርእሰ ጉዳዩ ጋር ተያይዞ በሚነሱ ሃሳቦች ዙሪያ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ አድርገዋል፤ እኛም እንዲህ አቅርበነዋል።

አዲስ ዘመን፦ ኢህአዴግ ከግንባር ወደ ውህደት መምጣት አለበት የሚሉ አስተያቶች ይሰነዘራሉ፤  እስከአሁን በግንባርነት መዝለቁ በፓርቲው እንዴት ይገመገማል ?

ወይዘሮ ሙፈሪያት ፦ ኢህአዴግ አራት ፓርቲዎች የመሰረቱት ድርጅት ነው። ለአንድ ፓርቲ መሰረታዊ ከሚባሉ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ፕሮግራም ነው። ፓርቲውን የመሰረቱት አባል ድርጅቶችም ፕሮግራም ከአንድ ምንጭ የተቀዳ ነው። ፓርቲዎቹ በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ አቋም፣ እምነትና  አመለካከት አላቸው። በአሰራርና በአደረጃጀትም የአገሪቱን ነባራዊው  ሁኔታ የሚወክሉ  ናቸው። ነባራዊ ሁኔታውን ያልመሰለ ፕሮግራም ውጤታማ አይሆንም። የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታዎች ለሚወጡት ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች ለሚወሰዱት አቋሞች መሰረታዊ መነሻና ምክንያት ናቸው።

የኢህአዴግ አደረጃጀት  ከነባራዊ ሁኔታ የተቀዳ መሆኑ ረጅም ርቀት ለመጓዝ አስች ሎታል።  ደርግን መደምሰስ ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡ በፀረ ድህነት ትግሉም ላይ በአንድ አስተሳሰብ በአንድ ልብ እንዲቆም ለማድረግ አግዟል።  ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲሰፍን መሰረት ጥሏል። የአገራችንን የድህነት ገፅታ ለመቀየር ያስቻለ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት እንዲፈጠር ያደረገ አደረጃጀት ነው። አደረጃጀቱ የሚገመገመው ከአመጣው ወጤት ይሆናል።

አዲስ ዘመን፦ አደረጃጀቱ ነባራዊውን  ሁኔታ መሰረት ያደረገ ነው ሲባል አባል ድርጅቶቹ ከታገሉላቸው አላማዎች መካከል በአገሪቱ የነበረውን የብሄር ብሄረሰቦች ጥያቄ ይወክላል?

ወይዘሮ ሙፈሪያት፦ ነባራዊ ሁኔታ የምንለው ኢህአዴግ ሲጠነሰስም ሆነ ሲጎለብት ይዟቸው  ከተነሳቸው አጀንዳዎች መካከል አንዱን ይወክላል። ይኸውም የብሔር ብሔረሰቦችን የእኩልነት መብት ማረጋገጥ ነው። በኢትዮጵያ ጠንካራ መሰረት የነበረው የብሄር ብሄረሰብ ጭቆና ነበር፡፡  የፖለቲካ ትግሉም አንዱ ጥያቄ የነበረው የብሔር ብሄረሰብ ጥያቄ ነው። ይሄንን ማንም ሊክደው አይችልም። ሁሉም «ሆ» ብሎ እንዲቆም ያደረገው የብሔር  ብሄረሰብ የመብትና የእኩል ተጠቃሚነት ጥያቄ ነው። ተማሪዎች ፣ አርሶ አደሮች ፣ ሴቶች ፣የሁሉም እምነቶች ተከታዮች ተዋድቀውለታል። ስለዚህ ይህን ጥያቄ በመሰረታዊነት ለመመለስ የሚያስችል ፕሮግራም፣ ሕገ ደንብ፣ አደረጃጀትና አሰራር ሊኖር ይገባል። ከነባራዊ ሁኔታ ጋር ያለው ዝምድና ይሄ ነው። ከነባራዊ ሁኔታ የመነጨ አገር በቀል መፍትሔ ነው ተብሎ መወሰድ አለበት።

አዲስ ዘመን፦ አሁን የብሔር ብሔረ ሰብ ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል፤ አደረጃጀቱ አያስፈልግም የሚል መከራከሪያ ይነሳል። በእዚህ ላይ ምን ይላሉ ?

ወይዘሮ ሙፈሪያት ፦ አዎ !  በወሳኝ መልኩ የብሄር ብሔረሰብ ጥያቄ ተመልሷል። በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 39  ዋስትና እንዲኖረውም ተደርጓል። ታዲያ ለምንድን ነው ጉዳዩ  አጀንዳ የሚሆነው? የሚለው መልስ ይሻል። አስተሳሰብ የነባራዊ ሁኔታ ነፀብራቅ ነው። በቀደሙት ዓመታት በስርዓትም ጭምር የተደገፈ  የገዥና የተገዥ መደብ  አስተሳሰብ ነበር። ይሄ አሁን ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ መሰረት የለውም።  ህሊናዊ ሁኔታዎች ግን አሉ፤ የዞሩ ድምሮችና የቀሪ አስተሳሰብ ወኪሎች አሉ። ሥርዓቱ ለሀሳብ ብዙህነት እድል የሚሰጥ ስለሆነ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላችሁ ከዛሬ ጀምሮ እዚህ ምድር ላይ መኖር አትችሉም አይባልም።

ሌላው ያለው ነባራዊ ሁኔታ ነው። የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካል ኢኮኖሚ መሰረታቸው የተሸነፈ ቢሆንም አሁንም ለዚህ የተመቹ  ጉዳዮች አሉ። በብሔር ስም እወክላችኋላሁ፤  ጥቅማችሁን አስጥብቅላችኋላሁ የሚል አካል አለ። የነባራዊና የህሊናዊ ሁኔታ ውጤቶችን ካየን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መሰረታቸው የተናደ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ተሸንፈዋል ማለት አይቻልም። በዴሞክራሲ የበለጸጉ የሚባሉ አገራት ጭምር ቀድሞ  የነበረው የቀኝ አክራሪ ኃይሉ የበላይነት ለመያዝ ጥረት የሚያደርግበትም አዝማሚያ እየታየ ነው። 

ስለዚህ እንደ አንድ ምክንያት ተወስዶ አደረጃጀት ከተጠቀሰው ጉዳይ አንጻር  ብቻ ነው ሊታይ ይገባዋል ማለት አይቻልም። ቁም ነገሩ ለህብረተሰቡ ለውጥ ማምጣት የሚችል አደረጃጀት ነው አይደለም የሚለው መሆን አለበት።

አዲስ ዘመን፦ አደረጃጀቱ የተለያዩ አስተያየቶችን ያስተናግዳል፤ ለአብነትም ህብረተሰቡ በአካባቢያዊ ጉዳዮች ብቻ እንዲያተኩር አድርጓል፣ አንድ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት እንቅፋት ይፈጥራል የሚሉት ይጠቀሳሉ። ጉዳዮቹ እንዴት ይታያሉ ?

ወይዘሮ ሙፈሪያት፦ መሬት ላይ ያለው እውነታ ምንድን ነው የሚለውን መመልከት ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ የትግል ታሪክና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሂደት ውስጥ የማንነት ጉዳይ መሰረታዊ ጥያቄ ነበር። አደረጃጀቱ ብሄር ብሄረሰቦች ትክክለኛ ማንነታቸውን እንዲያውቁ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። የተካደውን ማንነታቸውን በኢህአዴግ መሪነት በትግላቸው ለማረጋገጥ የሚያስችል ስራ ተሰርቷል። ትግሉ የብሄር ብሄረሰቦች መሰረታዊ የፖለቲካ ጥያቄ እንዲመለስ አድርጓል። ኢህአዴግ  ሥርዓቱ የፈጠረውን ችግር ሕዝቡን አስተባብሮና  አታግሎ ምላሽ እንዲያገኝ አድርጓል።

 የማንነት ጥያቄ  ማሳረጊያው የሕዝቦችን የመልማት አቅምና እድል ማውጣት መቻል ነው።  ስለዚህ ብሔር ብሔረሰቦች ያዋቀሯቸው ክልሎች ያላቸውን የመልማት እድል ተጠቅመዋል። የመብት፣ የማንነት፣ የመሬት ፣ የንብረት ባለቤትነትና ተጠቃሚነት ጥያቄ ያነሱ ነበር፤  እድሉን አግኝተዋል። ይህ በአካባቢ ጉዳይ ብቻ የማተኮርና  በሰፈር የመታጠር ጉዳይ አይደለም። ሁሉም አካባቢውን እያለማ  በጋራ የሚያድግበትንም መንገድም ያመቻቻል። በህገ መንግስቱም ሆነ በሚወጡት ህጎች የሚንጸባረቀው ይኸው ነው።

የፌዴራል ሥርዓቱ አንድነትን የሚያጠና ክር ነው። አደረጃጀቱ ህብረተሰቡ በአካባብያዊ ጉዳዮች እንዲታጠር አድርጓል የሚለው ከነባራዊ ሁኔታውም ጋር አይሄድም። የትኛው ብሔር ብሔረሰብ ነው ኢትዮጵያ አገሬ ሳይል ክልሌ ብሔረሰቤ  ብቻ ብሎ የሚቆመው?  የሩቅ ታሪክ ማስታወስ  አያስፈልግም። የኤርትራ ወረራ ባጋጠመበት ወቅት ከምሥራቅ- ምዕራብ፥ከሰሜን - ደቡብ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ነው የተነሳው። እንዲህ ዓይነት  የቆየ እሴት አለ። ይሄን ለመሸርሸር የሚያንዣብቡ አመለካከቶችና ድርጊቶች አሉ።  እነርሱ ላይ መስራት ይገባል። አስተያየቱ ግን ከነባራዊ ሁኔታው የመነጨ አይደለም።

አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በመሰረተ ልማት ሁሉንም አካባቢዎች ከማስተሳሰር ጋርም የተያያዘ ነው፤   እኩልነትንና አንድነት እያጠናከሩ ከመሄድ ጋርም ግንኙነት አለው።።  ኢንቨስትመንቱም የአካባቢዎችን እምቅ አቅምና ችሎታ በሚያወጣ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል እየተደረገ ነው። የአንዱ ውጤት ለሌላው ግብዓት ይሆናል። ኢኮኖሚውም፣ ፖለቲካውም ሆነ የፌዴራል ሥርዓቱ ይህንን የሚያስተናግድ ይሆናል በሚል እየተሰራ ነው። ኢህአዴግ  ከነባራዊ ሁኔታ ውጪ የሆነ መፍትሔ  አምጥቶም አያውቅም ።

አዲስ ዘመን፦  የአንድነት እሴቱን የሚሸረሽሩ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፤ የጠባብነትና የትምክህት አስተሳሰብ በፓርቲውም ሆነ በህብረተሰቡ ዘንድ ተስተውሏል። ጉዳዩን ከአደረጃጀቱ ጋር የሚያያይዙ አሉ፤ ተገቢ ነው?

ወይዘሮ ሙፈሪያት ፦ እንደነዚህ አይነት ዝንባሌዎች ከድርጅቱ ወደ ሕዝቡ፣ ከሕዝቡ ወደ ድርጅቱ ይመጣሉ።  ሕብረተሰቡ ኋላ ቀር አመለካከቶችን ባሸነፈ መጠን ጉዳዮች አጀንዳ አይሆኑም። ለዚህ ደግሞ ድርጅቱ ሁሌም መሪ ስለሆነ እነዚህን ኋላቀር አመለካከቶች እየለየ፣ እየታገለና እያረመ ከሄደ እንዲሁም የመሪነት ሚናውን ከተጫወተ  ይሄ ነባራዊ ሁኔታ ይከስማል።

 መሰረታዊ ምንጩ አመለካከት ነው። አደረጃጀትና አሰራር ይህን ችግር በማቃለል የራሱን ሚና ሊጫወት ይችላል።  ዋናው ግን አስተሳሰብ፣ አመለካከትና የንቃተ ህሊና ደረጃ ነው። ስለዚህ አደረጃጀቱ ነው የዚህ ምንጭ  ማለት በቂ ምክንያት አይደለም። ነባራዊ ሁኔታው የሚሸከመው አስተሳሰብ አለ። ስለዚህ የሕዝቡ የተወዳዳሪነት አቅም በሚፈለገው ደረጃ ከተገነባና  ለተለዋዋጭ ሁኔታዎች ሁልጊዜም ዝግጁ ከሆነ ዝንባሌዎቹ  እየተዳከሙ ይሄዳሉ፤ ቦታ አይኖራቸውም።

 ግለሰብ ፣ ቡድንና  አመራሮችም በደካማ ጎን ህብረተሰቡን ያነሳሳልኛል ብለው በሚያስቡት መንገድ ቅስቀሳ ሊያደርጉ ይሞክራሉ። ህብረተሰቡ ግን እኔ በአቋራጭ ሳይሆን በጥረቴ እሴት ጨምሬ ነው ማደግና መበልፀግ የምችለው የሚለውን አስተሳሰብ እምነቱ ማድረግ ከቻለ  መንግሥትና ድርጅት ተገቢ ሚናቸውን ከተወጡ አመለካከቶቹ ተቀባይ አያገኙም።

አዲስ ዘመን፦የአደረጃጀት ጉዳይ በጉባኤም ተነስቶ እንደነበር ይታወቃል፤  ምን አይነት አስተያየቶች ይንሸራሸሩ ነበር?

ወይዘሮ ሙፈሪያት፦  ድርጅቱ  ለሃሳብ ነፃነት በሚሰጠው ክብር ይሄ ጉዳይ አይነሳ አላለም። ዴሞክራሲያዊ ድርጅት እንደመሆኑ በተለያዩ ወቅቶች በሚኖሩ መድረኮች ሁሉ ይነሳል።  ሀሳቡ እያደገ መጥቶ በድርጅቱ የተለያ ጉባኤዎች ተንፀባርቋል። በእዚህም ምክንያት ግልፅ የሆነ አቅጣጫ  እንዲቀመ ጥለት ተደርጓል። ድርጅቱ አዲስ ሀሳብ ሲመጣ በጥናት የመመለስ ባህል አለው። ከዚህ አኳያ በጥናት እንዲመለስ የቤት ስራ የተሰጠው አዲስ ዲፓርትመንት ተቋቁሞ ጉዳዩን እንዲመለከተው ተወስኗል።  ሀሳቡ በጥናት እንዲመለስ አቅጣጫ ተቀምጧል።

መነሻው እድገታችንን ወደፊት ከማራመድ ካለማራመድ ጋር  የሚያያዝ ነው። አሁን የደረስንበትን ደረጃ እንዴት እንመልከተው? እንዴት አሻግረን እንይ? የሚለው የድርጅቱ መሰረታዊ መለያ ነው። የእድገት ደረጃውን የሚመጥን አደረጃጀት እንዴት ይኑረን ነው ጉዳዩ።

አዲስ ዘመን፦ በጥናቱ መነሻነት በሂደት ወደ ውህደት የሚመጣበት እድል ይኖራል ?

ወይዘሮ ሙፈሪያት፦ አደረጃጀት በባህሪው እንደየወቅቱ ሁኔታ ተለዋዋጭ   ነው -  የህብረተሰብ እድገትም እንደዚሁ። ስለሆነም የጥናቱም መነሻ ከዚህ ተለዋዋጭ ከሆነው የህብረተሰብ ፍላጎትና ጥያቄ ጋር አደረጃጀቱ  እንዴት ይሆናል የሚል ነው። መዋሃድ ያስፈልጋል አያስፈልግም የሚሉ ጉዳዮች ሲነሱ አሁን ከተደረሰበት እድገት ደረጃ አኳያ አሁን ያለው አደረጃጀት ምን ቅርፅና ይዘት ቢኖረው ነው የተሻለ የሚለው ሀሳብ ይንሸራሸራል። ይህን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ በሳይንሳዊ መንገድ ተጠንቶ ይወሰናል።

አዲስ ዘመን፦ ተግባራዊ የሚሆንበትን ወቅት  መገመት ይቻላል ?

ወይዘሮ ሙፈሪያት፦ ወደ ተግባር የማሸጋገር ጉዳይ ጥናቱን ተከትሎ ነው ሚመጣው።  ግምት ማስቀመጥ ይቸግራል። እውነተኛ ጥናት የሚሆነው ይዞት የሚመጣው ግኝት ነው።አደረጃጀትም ሆነ አመለካከት አዳጊዎች ናቸው። ስለዚህ አዳጊ ባህሪያቸውን ታሳቢ አድርጎ በምን አቅጣጫ ይደጉ? ህብረተሰብን እንዴት ሊያሳድጉ ይችላሉ? የሚሉ ጉዳዮች ታሳቢ ይደረጋሉ።  የመጀመ ሪያም የመጨረሻም መነሻና መድረሻችን የህብረተሰቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረ ጋገጥ ያስችላል የሚለው ነው መመዘኛው፡፡ መቼ ነው የሚተገበረው? ጥናቱ መቼ ተጀምሮ ያልቃል ?የሚሉ ዝርዝር ጉዳዮች እየተሰሩ ነው ያሉት።

   አደረጃጀት ነባራዊ  ሁኔታን  የሚሸከም  መሆን አለበት። አደረጃጀት የሚቀረፀው ተልዕኮ እንዲሸከም ነው። ስለዚህ ተልዕኮ የመሸከም ቁመና ያለው አድርጎ መስራት ያስፈልጋል። ለማንም ተብሎ የሚሰራ ሳይሆን ጊዜውም ህዝቡም የሚፈልገው ስለሆነ ነው። አሁን ይተግበር ቢባል አይቻልም። ለዚህ የሚሆን ነባራዊ ሁኔታ አለ ? ይህን አደረጃጀት የሚሸከም አስተሳሰብ ተፈጥሯል ወይ ? የሚለውን ማየትና መፈተሽ ስለሚጠይቅ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ይመለሳል፡፡

አዲስ ዘመን፦ ፓርቲው ሌሎች በጥናት ሊፈተሹ ይገባል ያላቸው ጉዳዮች አሉ ?

ወይዘሮ ሙፈሪያት፦ ብዙ ሊጠኑ የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ፈትሸናል። የጥናትና  ምርምር  ዲፓርትመንቱ አደረጃጀት የወራት እድሜ ቢያስቆጥርም ወደ ተጨባጭ ስራ ተገብቷል፡፡ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል የአደረጃጀት፣ የፓርቲ ጉዳዮችና ሌሎችም ተለይተው ወደ እንቅስቃሴ እየተገባ ነው። ስልታዊ በሆነ መንገድ ከረጅምና አጭር ጊዜ አኳያ ሊመለሱ የሚገባች ጉዳዮች ተለይተው በሂደት ላይ ይገኛሉ።

ፓርቲው የረጅም ጊዜ ግን ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት ጥረት እያደረ ነው። በፍኖተ ካርታው  ረጅሙን የህዳሴ ጉዞ የሚመራና እየመራ ድርጅት ነው። የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲጎለብትና  ሥር እንዲሰድ ማድረግ የሚያስችል የራሱን ሚና ለመጫወት ተዘጋጅቶ ያለ ድርጅት ስለሆነ እነዚህን ሁኔታዎች ከግምት ባስገባ መልኩ ከህብረተሰብ ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር ሊታዩ የሚገቡ የአደረጃጀት፣ የአሰራር፣ የአመለካከት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ባህሪ ያላቸው ጉዳዮች ላይም ለፓርቲው በሚኖረው ፋይዳና ትርጉም ልክ ሊታዩ ይገባል  ተብለው የተለዩ ጉዳዮች አሉ።

አዲስ ዘመን፦  አደረጃጀቱ በሂደት ቢስተካከል ከፌዴራል ስርዓቱና ከህገ መንግስቱ ጋር ተያይዞ ለውጥ ይኖር ይሆን?

ወይዘሮ ሙፈሪያት ፦  ሕገ መንግሥቱ የሁሉም ነገር ፍኖተ ካርታ ነው። ለሚወሰዱት ማንኛቸውም አቋሞችም ሆነ ለሚከናወኑ ስራዎች መሰረት ነው። በሚገነባው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕቀፍ ውስጥ ሊታዩ የሚገባቸው ጉዳዮች ካሉ ለለውጥ ዝግጁነት አለ።

አዲስ ዘመን፦  ለአደረጉልን ትብብር በጣም እናመሰግናለን !

ወይዘሮ ሙፈሪያት፦ እኔም አመሰግናለሁ!

 

ዳንኤል በቀለ

 

Published in ፖለቲካ

በኢትዮጵያ በጎማ ዛፍ የሚለማ 84 ሺ ሄክታር መሬት ይገኛል፤

አለፍ አለፍ ብለው ከተሰሩት ቤቶች ውጪ አካባቢው በአገር በቀልዛፎች ተሸፍኗል። ከነዚሁ ትላልቅ  ዛፎች ስር ደግሞ የቡና ተክል ይገኛል። አንዳቸው ለአንዳቸው የሚኖሩ እስከሚመስል ድረስ የቁንዶ በርበሬ ተክል ዛፎቹን ተደግፎ በመብቀሉ ደስ የሚል እይታን ይፈጥራል። ከዓመት እስከዓመት ልምላሜ የማይለየው ይኸው የበበቃ አካባቢን ተወዳጅ ከሚያደርጉት ተፈጥሯዊ ገፅታዎች  መካከል ይጠቀሳል፡፡

የጎማ ዛፍ ተክሎችን አልፈን ያገኘነው የጎማ ዛፍ ፕሮጀክት ሠራተኞች መኖሪያ እና እንደቢሮ የሚጠቀሙበት ቤት ሙሉ በሙሉ በቆርቆሮ የተሰራ ነው። በኬሚካል ኢንዱስትሪ ስር የሚተዳደረው የጎማ ዛፍ ልማት ፕሮጀክት በስፋት ባይሆንም ሥራ ከተጀመረ ረዘም ያለ ጊዜ ማስቆጠሩን ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚያመለክቱት፡፡

 የጎማ ዛፍ ምርት ወይም (Natural Rubber) ከጎማ ዛፍ ተክል ሚገኘው ፈሳሽ ወይም ላቴክስ በመሰብሰብ የሚገኝ ነው።  በኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የጎማ ዛፍ ፕሮጀክት ተወካይ ሥራ አስኪያጅ  አቶ ይታገስ እሸቱ እንደሚናገሩት፤  የጎማ ዛፍ ምርት  ከጎማ ዛፍ ተክል የሚገኘውን ፈሳሽ በመውሰድና በማጠራቀም ጥቅም ላይ የሚውለው በፈሳሽና በደረቅ መልኩ ነው።  ከጎማ ዛፍ የሚገኘው ምርት ለመኪና ጎማ መስሪያ እንደ ዋና ግብአት ያገለግላል። በተጨማሪም መጠናቸው እና የመለጠጥ ባህሪያቸው ከፍተኛ ለሆኑ መገልገያዎች እንደ ጓንት፣ ኮንዶም እንዲሁም ለጫማ ፋብሪካዎች፣ ለማሽን የሚያገለግሉ ቀበቶዎችንና  ለባቡር መስመር ግንባታ ይጠቅማል፡፡

 የጎማ ዛፍ ምርት በተፈጥሮው ተፈላጊነቱ ከኢኮኖሚ ዕድገትና መስፋፋት ጋር እንደሚያያዝ አቶ ይታገስ ይናገራሉ። ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች እየተበራቱ ሲመጡና የኢንዱስትሪዎች ተመጋጋቢነት ሲያድግ የተፈጥሮ ጎማ ዛፍ ምርት ፍላጎት ከፍ  የሚያደርገው መሆኑንም ነው የሚያስረዱት፡፡

በ1983 ጀምሮ ለአምስት ዓመት የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ኢትዮጵያ ለጎማ ዛፍ ምርት ሰፊ ቦታ እና አመቺ የአየር ሁኔታ እንዳላት ተረጋግጧል። በኢትዮጵያ 84ሺ ሄክታር መሬት በጎማ ዛፍ ለማልማት ምቹ መሆኑ ተለይቷል። ለጎማ ዛፍ ተክል ምርት ምቹ የሚባለው ቦታ የዝናብ መጠኑ ከፍተኛ የሆነና ሞቃታማ የአየር ንብረት  ነው። በዓለም በጎማ ምርት አምራችነት ከሚጠቀሱት አገሮች መካከል ታይላንድ፣ ኢንዶኔዢያና ህንድ ይጠቀሳሉ፡፡

በኢትዮጵያ ለጎማ ዛፍ ምርት ምቹ ሆነው የተመረጡ ቦታዎች ቴፒ፣ ኢሉባቦር፣ ጉራ ፈርዳ ናቸው። በጊዜው ከተመረጡት ቦታዎች መካከል ወደ ሥራ ለመግባት መሰረተ ልማት የተሟላለት በመሆኑ  ጉራ ፈርዳ ወረዳ  ተመራጭ የሆነ ሲሆን ሥራው በ1998 እንዲጀመር ተደርጓል። ከዚህ አንፃር በበቃ የሚገኘው የጎማ ዛፍ ልማት የሚፈለገውን ያህል አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት እንዳልሆኑ በጉብኝታችን ተገንዝበናል፡፡ ይሁንና ከሌሎች  አካባቢዎች ጋር ሲነጻጸር  የተሻለ በመሆኑ ፕሮጀክቱ እንዲጀመር መደረጉን ነው አቶ ይታገስ የሚያመለክቱት፡፡ ያም ቢሆን ግን  በተያዘለት እቅድና ጊዜ መሰረት እየሄደና ፕሮጀክቱ በተጠናለት መሰረት ውጤታማ  መሆን አለመቻሉንም ጨምረው አስረድተዋል፡፡

እንደአቶ ይታገስ ገለፃ፤ የጎማ ዛፍ ፕሮጀክት አሁን ያለበት ደረጃ እስኪደርስ ድረስ በርካታ  ተግዳሮቶች አጋጥመውታል፡፡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የነበረው የመንግሥት መለዋወጥ አንድ ችግር ነው። የመንግሥት ሥርዓት ሲቀያየር የፕሮጀክቱን ትኩረት ቀንሶታል። ሌላው ፕሮጀክቱ ከአንድ ድርጅት ወደሌላ ድርጅት ኃላፊነት በሚዘዋወርበት ወቅት በጀት በወቅቱ እና በአግባቡ የማግኘት ችግር ገጥሞታል። እንዲሁም እንደ መንገድ፣ መብራት፣ የፕሮጀክቱ ሠራተኞች መኖሪያ ቤት የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት አቅርቦት አልተሟ ሉለትም። እንዲሁም ተገቢ የሆነ የኢንቨስ ትመንት ማበረታቻ አለመደረጉ ከችግሮቹ መካከል ናቸው። ይህም ቢሆን ግን እስካሁን በጎማ ዛፍ ልማት ላይ የሚታየው ሥራና ውጤት በዘርፉ ብዙ ርቀት ከተጓዙት አገሮች አጀማመር ጋር ሲነፃፀር መጥፎ የሚባል አይደለም፡፡

የጎማ ዛፍ ምርት የሚመረተው በአካባቢው አርሶ አደሮች ነው። የአርሶ አደሮቹን መሬት ለጎማ ዛፍ ምርት እንዲውል ለአርሶ አደሮቹ የሚገኘውን ጥቅም በማሳወቅ ነው የተጀመረው። የጎማ ዛፍ ችግኞችን ቀደም ሲል ከማሌዥያ እና ከኮትዲቯር ዝርያዎችን በማምጣት ተተክለዋል። ችግኞችን ከውጭ ማምጣት ከፍተኛ ወጪን ይጠይቅ ስለነበር በአሁኑ ጊዜ ችግኞቹ እዚሁ ይዘጋጃሉ። ችግኞቹን ለማዘጋጀት ከሚወጣው ወጪ በጣም በዝቅተኛ ብር ለአርሶ አደሮቹ እንዲቀርብ ይደረጋል።

በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ  የጎማ ዛፍ ምርት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪን ማስቀረትና ለጎረቤት አገሮች  ምርቱን  ማቅረብ  ከፕሮጀክቱ ዋና ዋና እቅዶች መካከል ይጠቀሳል፡፡ ይሁንና የጎማ የተተከሉት ዛፎች ብዙ ስላልሆኑ ምርት ለመሰብሰብ የደረሱ ዛፎች ቁጥር አነስተኛ መሆን ለእቅዱ  መሳካት እንቅፋት እንደሚሆን ስጋት መፍጠሩን ነው አቶ ይታገስ የሚያስረዱት፡፡  ይህም ከፍላጎቱ አንፃር ምርቱ መሸፈን የተቻለው አምስት በመቶ ብቻ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ በቀጣይ የዛፎቹ ዕድሜ እየጨመረ ሲመጣና ከስር ከስር የሚተከሉት ችግኞችም ሲበራከቱ የምርት መጠኑ እየጨመረ ይመጣል የሚል ግምት ተይዟል፡፡

የጎማ ዛፍ ተክል ከሚሰጠው ምርት በተጨማሪ ለአካባቢ ጥበቃና ለአየር ንብረት የሚሰጠው ጥቅም ከሌሎች የዕፅዋት ዓይነቶች የተሻለ ነው። ከዚህም ባሻገር በጎማ ዛፎቹ መካከል ባለው ክፍት የጎማ ዛፍ ተክሉ ሦስት ዓመት እስኪሞላው ድረስ ሌሎች ዕፅዋትን በመትከል መሬቱን ለተጨማሪ ምርት መጠቀም ይቻላል። የጎማ ዛፍ ልማት የሚፈልገው የሠራተኛ ቁጥር ከፍተኛ  በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ዕድል በመፍጠርም የጎላ ሚና የሚጫወት መሆኑን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡

በቅርቡ ቴክሳ ሪሰርች የተሰኘ ድረገፅ ባወጣው መረጃ  እ.ኤ.አ በ2022 የኢትዮጵያ የጎማ ገበያ ፍላጎት ወደ መቶ 80 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያድግ አስታውቋል።  ካለፈው ዓመት በመነሳት የኢትዮጵያ የጎማ ፍላጎት እያደገ መምጣቱን ያመለክታል። ምክንያቱ ደግሞ የመኪኖች ቁጥር መጨመር፣ የመኪኖች መገጣጠሚያ እና ሽያጭ መጨመርና የውጭ አገራት በኢትዮጵያ ጎማ ማምረት ላይ በስፋት መሰማራት ነው። አያይዞም የግንባታ እንቅስቃሴዎች መጨመር፣ የህዝብ ትራንስፖርት ተጠቃሚነት መጨመርና ኢንዱ ስትሪያላይዜሽን እያደገ መምጣትና የመግዛት አቅም እየጨመረ መምጣቱንም ለጎማ ገበያ መጨመር እንደማሳያ ያነሳል።

ለአካባቢ እንዲሁም ለአገር ኢኮኖሚ ጥቅም የሚሰጥ ፕሮጀክት ላይ የባለሀብቶች ተሳትፎ እስከዛሬ ድረስ አነስተኛ መሆኑን የዘርፉ ተንታኞች ያመለክታሉ፡፡ በኢትዮጵያ ብቸኛ የጎማ አምራች የሆነው ሆራይዘን አዲስ ለጎማ ምርት ከሚጠቀመው ጥሬ እቃ ከፍተኛ ድርሻ ያለው የተፈጥሮ ጎማ እንደሆነ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አካለወልድ አድማሱ ይህንን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡

እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ፋብሪካው የጎማ ዛፍ ባለሙያዎችን ከህንድ በማስመጣት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ባለሙያዎች ስልጠና እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል። በስልጠናውም ምርትን በብዛትም በጥራትም ለመጨመር ከችግኝ ተከላ፣ ከእንክብካቤ፣ ከምርት ስብሰባ፣ ከክምችት እስከ ማጓጓዝ ድረስ ያለውን ሂደት እንዲሰለጥኑ እያደረገ ነው።

ፕሮጀክቱ ለድርጅታቸው የሚሰጠው ጥቅም አንድ በመቶ ያህሉን እንኳን እንደማይሸፍን ይናገራሉ። ‹‹ለፋብሪካው ሊያበረክት ከሚችለው ጥቅም በላይ ፕሮጀክቱን የጀመረው የቀድሞው ማታዶር አዲስ ጎማ በመሆኑ እንደ ድርጅት ብቻ ሳይሆን እንደ አገርም ኃላፊነት እንዳለብን በማሰብ ነው ለፕሮጀክቱ ድጋፍ የምናደርገው›› ይላሉ።

ከኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ኮርፖሬሽኑ የጎማ ዛፍ ፕሮጀክት ላይ ያስፈልገኛል የሚለውን ድጋፍ ለሆራይዘን አዲስ በማቅረብ የስልጠና እና የእቃ ድጋፍ እንዲሁም ማንኛውንም የአስፈላጊ እገዛን ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አቶ አካለወልድ አድማሱ ይናገራሉ። ድርጅታቸው  የጎማ ዛፍ ፕሮጀክቱ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ ማገዝ የጀመረው ሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው። እስከዛሬም ለፕሮጀክቱ የተሰጠው ትኩረት ሊያስገኝ ከሚችለው አገራዊ ጥቅም አንፃር ሲታይ አነስተኛ ቢሆንም፤ በቂ የሆነ እገዛና ትኩረት ቢሰጠው የሚፈለገው ደረጃ ላይ መድረስ ይቻላል ባይ ናቸው።

እስካሁን ከፕሮጀክቱ የሚቀበሉት የተፈጥሮ ጎማ ምርት ለሚያመርቱት ጎማ የሚፈለገውን ያህል ጥራት እንዳልነበረውም ያስረዳሉ። ጥራቱን ያልጠበቀ ቢሆንም ምርቱን በዓለም አቀፍ ዋጋ እንደሚገዙትም ይናገራሉ። አሁን ላይ በጎማ ዛፍ ምርቱ ላይ የሚታይ የጥራት መስተካከል እንዳለና ነገር ግን በቂ አለመሆኑንም ያምናሉ። ጥራት በአንድ ጊዜ እንደማይመጣና እስካሁን ያለውን መሻሻል በማየት ወደፊት ከአሁን የተሻለ ጥራት እንደሚያመጣ ይጠበቃል። የፕሮጀክቱ ሠራተኞች የሚኖሩበትንና የሚሰሩበት ቦታ ያለውን ችግር በማየት ‹‹በአንድ እጅ ተይዘው ነው እየሰሩ ያሉት›› በማለት ለፕሮጀክቱ እየተሰጠው ያለው ለውጥ አነስተኛ መሆኑን ይገልፃሉ።

ከዚህ ቀደም ከውጭ በመጡ የጎማ ዛፍ ምርት ባለሙያዎች በተሰጣቸው ስልጠና ፕሮጀክቱ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች በቂ ዕውቀትን አግኝተዋል። በቅርብ ጊዜም ሁለተኛ ዙር ስልጠናን ከህንድ በመጡ ባለሙያዎች የሃሳብም የተግባርም ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። በአሁኑ ጊዜም  ብቁ የሆኑ 11 ባለሙያዎች ፕሮጀክቱ ላይ እየሰሩ ይገኛሉ።

በቀጣይ ከዘርፉ የሚገኘውን ምርት ጥራቱን እና አቅርቦቱን ለማሳደግና የውጭ ምንዛሪን እዚሁ ለማስቀረት ባለሙያዎቹን በመጠቀም የተሻለ ሥራን ለመሥራት ጥረት በኦሮሚያ ክልል ቦረና ለጎማ ዛፍ ምርት አመቺ የሆነውን ቦታ ሥራ ላይ ለማዋል ዝግጅትና በጎማ ዛፍ ምርት ላይ የጥራት ማሻሻል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡  

አገሪቱ  የጎማ ዛፍ ለማምረት የሚያስችል ሰፊ መሬት፣ በቂ የሰው ኃይልና ምቹ የአየር ንብረት ያላት ቢሆንም ዛሬም ድረስ ለዘርፉ  የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ የሚገባውን ጥቅም ማግኘት አልተቻለም፡፡ በመሆኑም የዘርፉ ባለድርሻ አካላትና ባለሀብቶች ለጎማ ዛፍ ልማት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይገባል፡፡

 

ሰላማዊት ንጉሴ

 

Published in ኢኮኖሚ

 

ኬንያን ከሶማሊያ በሚያዋስነው ድንበር ላይ አንድ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ይገኛል፡፡ በዚህ ስፍራ በርካታ ሶማሊያዊያን ከውቂያኖስ ማዶ ተሻግረው ዘመዶቻቸውን የሚያቅፉባትን ቅፅበት ለዓመታት ሲናፍቁ ኖረዋል፡፡  ወደ ኋላ የመመለስ ቅንጣት ምኞት ወይም ፍላጎት የላቸውም፡፡ በመጠለያ ጣቢያው የቱንም ያህል ከባድ የመከራ ጊዜ ቢኖራቸው ‹‹ስቃይ በቃኝ›› ብለው ወደ አገራቸው መመለስን በጭራሽ አይፈቅዱም፤ አያስቡም፡፡ ሰሞኑን ታዲያ እንዲህ ባለ መልኩ ለዓመታት ከርመው ልክ የሚናፈቁት ቀን መድረሱን በተረዱ ጊዜ ድንገት ከወደ አሜሪካ የሰሙት ዜና ወሽመጣቸውን በጠሰው፡፡

ከሳምንት በፊት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ‹‹እግራችሁ አገሬ ድርሽ እንዳይል!›› ሲሉ ካገዷቸው ሰባት አገሮች አንዷ ሶማሊያ ነበረች፡፡ ሶማሊያዊው ስደተኛ አሕመድ አሰን ከአገሩ ሲወጣ ለጉዞ ስንቅ ይሆነው ዘንድ መኖሪያ ቤቱን ሸጧል፡፡ ስለዚህ ለእርሱ ወደ አገሩ መመለስ ጎዳና መውደቅ ነው፡፡ እናም ከዓመታት ትእግስት በኋላ ሕጋዊ የወረቀት ጉዳዮችን አጠናቆ አሜሪካ የሚያደርሰውን ቲኬት ለመቁረጥ  እየተሰናዳ በአለበት ወቅት የተሰማው ‹‹ባለህበት ቁም›› የሚለው የትራምፕ እገዳ ዱብ እዳ ሆኖበታል፡፡ በወቅቱ የሚይዝ የሚጨብጠውን ያጣው አሕመድ፤ ከቀናት በፊት ቃሉን ለዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ሲያቀብል ‹‹ከፍተኛ የኪሳራ ስሜት ይሰማኛል›› ነበር ያለው፡፡     

ይሄ የብዙ አገሮች ዜጎች የእለት ተዕለት እውነት ነው፡፡ ልክ እንደ አሕመድ ሁሉ ‹‹አዲስ ቀን ፍለጋ›› በሚል ‹‹ጉም ዘገና›› ብዙ ስደተኞች በተለያዩ ጣቢያዎች ስቃይን ይገፋሉ፡፡ ለረጅም ዓመታት በርካታ ምክንያቶችን ከጊዜያዊ ስንቃቸው ጋር በጀርባቸው አዝለው ውቂያኖስ የሚያቋርጡ ስደተኞች በየመንገዱ ወዳድቀው ሲቀሩ ታይተዋል፡፡ ለእነዚያ ስቃዮች የተሰጠው ትኩረት ግን በፍጹም የአሁኑን ያህል ነው ብሎ ለመቀበል ያዳግታል፡፡ ሆኖም የምንም ነገር መነሻው ከወደ አሜሪካ ከሆነ ተራ ወሬ ሳይቀር ‹‹ዜና›› ይሆናልና የስደተኞች ጉዳይ ዳግም የውይይት አጀንዳ ለመሆን ችሏል፡፡

ከሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ የመን፣ ሊቢያ እንዲሁም ሶሪያ ከመሳሰሉ አገሮች የሚነሱ ስደተኞች ለዓመታት ያለፉበትን የስቃይ ጉዞ ለመግታት በቂ ርቀት ሳያስኬድ፤ በአንፃሩ የአሜሪካ ጉዞ ጊዜያዊ እገዳ መነጋገሪያ ለመሆን በቅቷል፡፡ በእርግጥ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደፈለጉት በእስልምና ሀይማኖት ተከታይ አገሮች ላይ የእገዳ እርምጃውን በቀላሉ ለመተግበር አልቻሉም፡፡ ሁኔታውን ለቀናት ሲመረምር የቆየው የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእገዳው ላይ ሌላ እገዳን አስቀምጧል፡፡

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የትራምፕን እገዳ ተከትሎ በረራቸው ተስተጓጉሎ ለነበሩ ባለ ቪዛ ተጓዦች ቢያንስ ጊዜያዊ እፎይታን ሰጥቷል፡፡ ከእነዚህ ተጓዦች መካከል ከሦስት ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ቤተሰቡን ለመጎብኘት ካርቱም ጎራ ያለው ሱዳናዊ ዶክተር ከማል ፋድላል አንዱ ነበር፡፡ ዶክተሩ ‹‹አገር ሰላም›› ብሎ በወጣበት ቅፅበት የተላለፈው የትራምፕ አስደንጋጭ እገዳ ቀናትን በስጋት ታጥሮ አየር መንገድ እንዲያሳልፍ አስገድዶታል፡፡ ምስጋና ለፍርድ ቤቱ ‹‹የእገዳ እገዳ›› ይግባና በጥልቅ ስጋት ውስጥ የከረሙት የዶክተሩ ቤተሰቦች በመጨረሻ ኬኔዲ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተቃቅፈው በደስታ አንብተዋል፡፡ ዶክተር ከማልም ‹‹በፍርድ ቤቱ ማሸነፍ እጅግ ተደስቻለሁ፤ አሁን ወደ ስራዬ ለመመለስ ጓጉቻለሁ›› ሲል ስሜቱን አጋርቷል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዓለም ለስደተኞች ያላት አተያይ በእጅጉ ተቀይሯል፡፡ ከበዙ ውስብስብ ችግሮች ጋር ተዳምሮ አገሮች በተለይም አውሮፓውያኑ ከዜጎቻቸው ‹‹ጥቅም መነካት›› ጋር ተያይዞ ስደተኞችን የሚያገል አቋም ማንፀባረቁን ገፍተውበታል፡፡ የአውሮፓውያኑ አልበቃ ብሎ ‹‹በስደተኞች የተገነባች አገር›› በምትባለው አሜሪካ ሳይቀር ፀረ ስደተኛ አቋም መንፀባረቁ ጉዳዩን ቆም ብሎ ለመመልከት የሚያስገድድ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም ወትሮም ቢሆን በውስጥ ስቃያቸው ማብቂያ ያጡት የሶሪያ፣ ሊቢያ፣ የመንና ኤርትራ ስደተኞች ላይ ሌላ ጣጣ መደቀኑ የማይቀር ነው፡፡

ሰሞኑን በማልታ ተሰብስበው ሲመክሩ የከረሙት የአውሮፓ ሕብረት አባል አገሮች መሪዎች ካስተላለፉት ውሳኔ መካከል አንዱ የስደተኞች ጉዳይ ነበር፡፡ 28 የሕብረቱ አባል አገሮች በጋራ የተስማሙበት ጉዳይ በተለይም ከሊቢያ የሚጎርፉ ስደተኞችን ለመቀነስ ያለመ ነው፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ወደ አውሮፓ ለመሸጋገር በሚደረገው ጥረት በለስ ቀንቷቸው ከሚገቡት ይልቅ በውቂያኖስ የሚቀሩት ይበዛሉ፡፡ ለአብነትም ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ብቻ በ24 ሰዓት ከአንድ ሺ 750 በላይ ስደተኞች በኢጣሊያን ባሕር ጠባቂዎች ከተጋረጠባቸው ከባድ አደጋ መትረፍ ችለዋል፡፡ በመሆኑም የአገራቱ አዲስ ስምምነት ማጠንጠኛ ዘላቂ የሆነ የስደተኞች ቁጥጥር ፖሊሲ በማዘጋጀት የሕብረቱን አገሮች ድንበር ጥበቃ ማጠናከር የሚል አንድምታ አለው፡፡

በእርግጥ አገሮቹ ይሄን ዕቅድ ሲያስቀምጡ ጎን ለጎን ሊተገብሩ ያሰቧቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ቀዳሚ ስጋታቸው ሊቢያ እንደመሆኗ የሊቢያን የባሕር ላይ ጠባቂዎች ስልጠናና የግብዓት አቅርቦት ድጋፍ ማሳደግ ነው፡፡ የጋራ አቅምን በማሳደግ የሕገወጥ ዝውውር መተላለፊያዎችን መዝጋት፤ በሊቢያ የሚገኙ የስደተኛ መጠለያ ማዕከላትን በድጋፍ ማጠናከር፤ ከአገሪቱ አቅራቢያ ለሚገኙ አዋሳኝ አገሮች ድጋፍ በማድረግ የስደተኞች ፍሰቱን መቀነስ እንዲሁም በስደተኞች መሸጋገሪያ አካባቢ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ኢኮኖሚያዊ አቅም በማሳደግ በጉዳዩ ላይ ተባባሪ እንዲሆኑ ማድረግ የሚሉት ዕቅዶች በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡

ምንም እንኳን አገሮቹ ለክልከላው ተግባራዊነት የጋራ ስምምነት ቢኖራቸውም ጉዳዩን በመቃወም ነቀፌታቸውን የሰነዘሩ አልጠፉም፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው ከነዚህ ተቃዋሚዎች አንዱ የሆነው አምንስቲ ኢንተርናሽናል ውሳኔውን ‹‹ዘግናኝ ስቃይ›› ሲል በትዊተር ገጹ አስፍሮታል፡፡ መረጃው እንደሚያመለ ክተው ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ 180 ሺ ስደተኞች የኢጣሊያን ምድር ረግጠዋል፡፡ በተቃራኒው 4 ሺ 500 ንፁሀን ስደተኞች በሜዲትራኒያን ባሕር ሰጥመው ቀርተዋል፡፡ ከዚህ አሳዛኝ እውነታ ባሻገር ወዲያ ናይጄሪያውያን ስደተኞች ቦኮሀራም በተሰኘው አሸባሪ ቡድን ተገፍተው ሲፈናቀሉ ወዲህ ከኤርትራ ፀረ ወጣት የሆነው አገዛዝ ለበርካቶች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት መሆኑን ቀጥሏል፡፡ ከየትኞቹም አገሮች በላይ ግን ሊቢያውያን ቅድሚያውን ይዘዋል፡፡

በእርግጥ የሕብረቱ አባል አገሮች በስደተኞች ላይ መያዝ የጀመሩት መረር ያለ የጋራ አቋም ከሁኔታዎች መወሳሰብ አንፃር ተጠባቂ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም የስደተኞች ጫና በአለም አገሮች ላይ በርካታ ለውጦችን እያመጣ መሆኑን ቀድመው ተረድተዋል፡፡ በታይም መፅሔት የውጪ ጉዳዮች አምደኛው ኢያን ብሬመር ሰሞኑን ባወጣው ሰፊ ዘገባ እንዳተተው፤ የስደተኞች ጉዳይ ሲነሳ ምናልባት ብዙዎች የሚያስቡት የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና አገሮችን ቢሆንም ስጋቱ ግን የብዙ አገሮችን ቤት እያንኳኳ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ለዚህም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት ዋቢ በማድረግ እ.አ.አ 2015 ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ 65 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሰዎች በአስገዳጅ ሁኔታ ከመኖሪያቸው ሊፈናቀሉ ችለዋል፡፡

በዘገባው መሰረት አሁንም በጦርነት መፈራረሷ የቀጠለው ሶሪያ የተፈናቃዮቹን የአንበሳ ድርሻ ብትወስድም የተፈጥሮ ሀብቷ ከፀጋ ይልቅ እርግማን የሆነባት ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን በሁለተኝነት አስቀምጧል፡፡ በመቀጠል ከሀይማኖት ግጭት ጋር ተያይዞ ማይናማር ስትቀመጥ እ.አ.አ 1960 ነፃነቷን ካገኘች ጀምሮ አምስት ጊዜ መፈንቅለ መንግስት የተካሄደባት መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ዜጎቿ በብዛት ተፈናቅለዋል፡፡ ከእርሷ በመቀጠል በውትድርና ግዳጅና ሌሎች አስከፊ በደሎች ምክንያት ለወጣቶቹ የእግር እሳት የሆነው የኤርትራው መንግስት ዛሬም ዜጎቹን ለባሕር መገበሩን ቀጥሏል፡፡ ከኤርትራ በመቀጠል ኮሎምቢያውን ተጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ስደት ዓለም አቀፍ ችግር ነው፡፡ ነገር ግን ከኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችና ከተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶች ጋር ተያይዞ የአውሮፓና ሌሎች የአደጉ አገሮች ዜጎች ጣት ስደተኞች ላይ መቀሰሩን ቀጥሏል፡፡ በተቃራኒው ስደት እንዳይቀንስ አገሮች በውስጥ ሰላም እጦት መናጣቸው አልተቋጨም፡፡ በሁለቱ ግፊቶች መካከል ፍዳቸውን የሚገፉ ምንዱባን ከአገርም ከስደትም ሳይሆኑ በወጡበት ይቀራሉ፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አደባባይ ወጥቶ ‹‹የታክስ ከፋይ ዜጎቼን ሃብት ለመጠበቅ የስደተኝነት ሕጎችን አጠብቃለሁ›› ቢልም ውስጥ ውስጡን የዚህ አቋም ደጋፊዎች መበራከታቸው ይነገራል፡፡ በተለይም ወግ አጥባቂ የአውሮፓ አገሮች ፖለቲካ አራማጆች ፀረ ስደተኛ አቋማቸው ውሎ እያደር ገሃድ ወጥቷል፡፡ በመሆኑም ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ ለሚገኘው ስደት መፍትሄውን ማሰብ ክምር ተራራን የመግፋት ያህል እየከበደ መምጣቱ የማይቀር ነው፡፡

ይሁንና አሁንም ሆነ ወደፊት መፍትሄው ያለው ስደተኞችን ከሚቀበሉት አገሮች ዘንድ ብቻ ሳይሆን ስደተኞቹ ከሚፈናቀሉባቸው አገሮች መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የአውሮፓ ሕብረት አገሮች ‹‹የሚመጡብንን ስደተኞች እናቁም›› በሚል ለመምከር ሲቀመጡ ‹‹ዜጎቼን እንዴት ከስደት ላስቁም?›› ብሎ የሚያስብ አገር መኖር አለበት፡፡

 

ብሩክ በርሄ

Published in ዓለም አቀፍ
Thursday, 09 February 2017 18:59

ተሃድሶው እና ወጣቶች

ወጣቱ ትውልድ ትኩስ ኃይል፣ አገር ተረካቢና ታላቁን ኃላፊነት የሚሸከም የሕብረተሰቡ ክፍል መሆኑ ይታወቃል። በየትኛውም አገር ወጣቱን ያላቀፈና ያላሳተፈ እንቅስቃሴ የተፈለገውን ግብ አያሳካም የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ መንግስትም በጥልቅ ተሃድሶው ሂደት የወጣቱን ተሳታፊነትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መርሃ ግብሮችን እንደሚተገብር ያስታወቀው ይህንን ታሳቢ በማድረግ ነው።

ኢህአዴግ ወደ አዲስ አበባ ሲገባ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 52 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፤ ዛሬ ከ25 አመታት በኋላ 100 ሚሊዮን እንደደረሰ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከአጠቃላዩ  ሕዝብ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ወጣቱ ነው፡፡ ይሄ ቁጥር  በተወሰኑ አመታት ውስጥ ከፍ እንደሚል ይገመታል።

መንግስት በተለያዩ ወቅቶች በተደጋጋሚ እንደገለፀው ከሕዝቡ ቁጥር መጨመር ጎን ለጎን ይሄንን ሊሸከም የሚችል ብሔራዊ ኢኮኖሚ መገንባት ወጣቱን በከፍተኛ ደረጃ አሳታፊና በኢኮኖሚው ውስጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወት ማድረግ የጥልቁ ተሀድሶ ቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በነበሩት አመታት ወጣቱን በአነስተኛና ጥቃቅን ማሕበራት በማደራጀት ከመንግስት ብድርና ቁጠባ ተቋም ገንዘብ አግኝተው ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ  ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡

በዚህም መነሻነት ባገኙት ድጋፍና ብድር በመላው የአገሪቱ ክፍሎች በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ራሳቸውን የቻሉ፤ ከራሳቸውም አልፈው ለሌሎች ዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ በካፒታል አቅማቸውም የደረጁ መለስተኛ ፋብሪካዎችን ለመመስረት የበቁ ወጣት ኢንተርፕሬነሮችን በስፋት ማፍራት ተችሎአል፡፡ በጥልቅ ተሀድሶው ለወጣቶች በተሰጠው የተለየ ትኩረት መንግስት ይህንን የሕብረተሰብ ክፍል የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ በመላው ሀገሪቱ 10 ቢሊዮን ብር መድቦ የየራሳቸውን ስራ መስራት የሚችሉበትን ሁኔታዎች አመቻችቷል፡፡

ስራን  ሳይንቁ የሚሰሩ፣ የፈጠራ ችሎታቸውን በመጠቀም አዳዲስ ግኝቶችን የሚያበረክቱ እንዲሁም  ራሳቸውን ለውጠው ሕብረተሰቡንም በስራ ተነሳሽነትና ፈጠራ የሚለውጡ ወጣቶችን አገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ማየት የምትፈልገው  አሁን ነው፡፡

በአለማችን አዳዲስ የስራ ፈጠራ ባለቤቶችና ሀሳብ አመንጪዎች በመሆን እንዲሁም  በአገር ግንባታና ልማት በግንባር ቀደምትነት ትልቁን ድርሻ በመወጣት የሚጠቀሱት ወጣቶች ናቸው፡፡ በአገራችንም ቀደም ሲል የነበረው «ተምረናልና  መንግስት ስራ ያስገባን» የሚለው አመለካከት ለውጥ እያመጣ ቢሆንም በሌሎች ዘንድ እንደሚታየው በተነሳሽነት ለስራ ፈጠራ እራስን የመስጠት ዝንባሌ  መጎልበት አለበት። አገሪቱ ከምትከተለው የነጻ ገበያ የኢኮኖሚ ስርዓት አንጻር የሚበረታታው ዜጎች በአላቸው አቅም ወይም በማሕበር ተደራጅተው ከመንግስት ብድር በመውሰድ የራሳቸውን ስራ በመፍጠር ራሳቸውንና ሕብረተሰቡንም ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉበትን መንገድ ማስላትና መከተል ነው፡፡

መንግስት ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል የልማቱ ዋና አንቀሳቃሽ በመሆን በስራ ፈጠራ እንዲሰማራ እድሉን ሲያመቻች ወጣቱም ቀደም ሲል የነበረውን የአመለካከት ክፍተት በመድፈን እድሉን በአግባቡ  ለመጠቀም  አቅሙን ማጎልበት አለበት፡፡ በአለው የተወሰነ አቅም ለሁሉም ወጣቶች የሚሆን ስራ በመንግስት ተቋማት አይኖርም፡፡ ከፍተኛ የስራ እንቅስቃሴ የሚገኘው በግሉ ክፍል ኢኮኖሚ ሲሆን ስራ ፈጥሮ የድርሻን ለማበርከት ከፍተኛ ተነሳሽነትና ጥረት ማድረግ ይገባል። በእነዚህ ተቋማት በተወዳዳሪነት ለመቀጠርም አቅምን ማጎልበት ግድ ይላል።

መንግስት ሊያደርግ የሚችለው ትናንት እንዳደረገውና ዛሬም በማድረግ ላይ እንደሚገኘው ሁሉ ወጣቶች እየተደራጁ የራሳቸውን ስራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ፕሮፖዛል (የስራ እቅድ ፕላን) አውጥተው በዚሁ መሰረት የገንዘብ ብድርና ድጋፍ አግኝተው ስራ እንዲከፍቱ፤ ሰርተውም ራሳቸውንና ሕብረተሰቡን እንዲጠቅሙ ማስቻል ነው፡፡

ወጣቱን ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በተዘረጋው መርሃ ግብር ቀድም ብለው የታዩትን ጉድለቶች በማስታወስ የሚታረሙበትን መንገድ ከወዲሁ ማበጀት ይገባል። ቀድም ሲል በታየው ተጨባጭ ልምድ አንዳንድ ወጣቶች ተደራጅተው መንግስትን ብድር ጠይቀው ተፈቅዶላቸው አግኝተው ስራ ይከፍታሉ፤ ሰርተው ይኖራሉ ሲባል ገንዘቡን ተከፋፍለው ወስደው በማጥፋት ያባከኑ ተመልሰውም ለቤተሰብና ለሕብረተሰብ ሸክም የሆኑ ታይተዋል። ችግሩ እንዳይደገም ገንዘቡን ከመስጠት ጎን ለጎን ጥብቅ ክትትልና ገንቢ የሆነ ድጋፍ ያስፈልጋል።

ተበድሮ ለአልባሌ ጉዳይ ገንዘቡን መጠቀም ቤተሰብን፣ ሕዝብን፣ ሀገርን በእጅጉ የጎዳና የሚጎዳ  በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ከአለፉት ልምዶች በመቅሰም ከፍተኛ ትኩረትና ጥንቃቄ እንደሚደረግ ተመልክቷል፡፡ ገንዘቡ በትክክል የታቀደለት ስራ ላይ ለመዋሉ በየቀጠናው የወጣቶች ፕሮጀክቶችን እግር በእግር የሚከታተሉ ቢሮዎች ይቋቋማሉ፡፡ አንድም በትክክል በስራ ላይ መዋላቸውን ለራሳቸውም ለሕብረተሰቡም በሚጠቅም መልኩ መሰራት አለመሰራቱን ላልተፈለገ ጉዳይ መዋል አለመዋሉን የሚቆጣጠር ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ገንዘቡ በብድር ከመንግስት  የሚገኝ እንደመሆኑ መጠን ሰርተው ወጣቶቹ አግኝተው ተለውጠው አትርፈው ደረጃ በደረጃ በተቀመጠለት የጊዜና የአከፋፈል መጠን  ላበደራቸው ተቋም የሚመልሱት ነው፡፡

ይኸው ገንዘብ ተመልሶ ለሕብረተሰቡ አገልግሎትና ልማት የሚውል በመሆኑ ወጣቶች በከፍተኛ ሀገራዊ የኃላፊነት ስሜት ጥንቃቄ ሊያደርጉበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡  ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች፤ ደላላዎች ጭምር ይህን የወጣቱን ሕይወት ለመለወጥ በመንግስት በኩል ለስራ የተዘጋጀውን ገንዘብ ከበስተጀርባ ሆነው ሆነው ለመቀራመት የተለያዩ ውጥኖችን ከማዘጋጀት ወደ ኋላ እንደማይሉ ይታወቃልና።

ወጣቱ ሕይወቱን፣ ኑሮውን አካባቢውን ብሎም አገርን መለወጥ በሚያስችለው በዚህ የተለየ አጋጣሚ ውስጥ እድሉ በብልጣብልጦች እንዳይነጠቅ ደግሞ ደጋግሞ ማሰብ፣ መጠንቀቅ ገንዘቡን በተገቢው እቅድና ፕላን መሰረት በተጨባጭ ስራ ላይ ማዋል መቻል ይጠበቅበታል፡፡ እንደነዚህ አይነት እድሎች ተመልሰው ሊገኙ አይችሉምና፡፡

ወጣቱ መንግሥት ለጀመረው ጥልቅ ተሐድሶ  ግንባር ቀደም ተሳታፊና አጋዥ ሀይል ስለሆነ የበኩሉን ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ መንግሥት ወጣቱ የዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም በማሰብ  የሚኖር አዳዲስ የለውጥ ሐሳቦችን የሚይዝ የትኩስ ጉልበት ባለቤት በመሆን ሀገሩን በማልማትና በማሳደግ ረገድ መሪ ተዋናይ ሁኖ መስራት እንዳለበት ያምናል፡፡

በተፈጠረው የመልካም አስተዳደር እጦትና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ምክንያት ወጣቱ ትልቅ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን መንግስት በውል ተገንዝቦ በጥልቅ ተሀድሶ ልዩ ትኩረት ሰጥቶታል፡፡ ቀደም ሲል በታየው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተሳታፊ በመሆን መንግሥትን ጨምሮ በግለሰቦችና ቡድኖች ሀብትና ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱት በአብዛኛው ወጣቶች የመሆናቸው እውነት ሲታይ ከስራ ማጣት የተነሳ ለተቃዋሚዎች መሳሪያ መሆናቸውን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

መንግስት ይህን መሰረታዊ ችግር ለመፍታት በጥልቅ ተሐድሶው አማካኝነት ወጣቱን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ገንቢ ስራ ለመስራት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም በወጣቶች ፓኬጅ ተይዘው ተግባራዊ ሳይሆኑ የቆዩ ተግባራትን ለመፈጸም በርካታ ስራዎችን እየሰራም ሲሆን የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድን ማቋቋም እንደሚገባ አምኖበት ተግባራዊ አድርጓል፡፡

ቀደም ሲል የነበረው ችግር የፋይናንስ አቅም እጥረት ቢሆንም፤ እስከዛሬ ባንኮች የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና የመሳሰሉት ለወጣቶች የሥራ ፈጠራ የሚሆን ገንዘብ በመስጠት ረገድ የየበኩላቸውን አድርገዋል፡፡ ከተጨባጩ የወጣቶቻችን መሻትና ፍላጎት አንጻር በፊት የነበረው የኢኮኖሚ አቅም በቂ ሁኖ ባለመገኘቱ መንግሥት 10 ቢሊዮን ብር በመመደብ የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ እንዲቋቋም አድርጓል፡፡ ነገር ግን ይሄንን ፈንድ ለማቋቋም የዘገየ ቢመስልም ቀድሞም በመጠናት ላይ የነበረ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ለሀገራችን ወጣቶች ችግር አቅም በፈቀደ መጠን ችግር ፈቺ፣ አምራች፣ አትራፊና ተጠቃሚ ሰራተኛ ዜጋ እንዲሆኑም የሚያስችል ነው፡፡

ወጣቶች ሊሠሩአቸው የሚገቡ ስራዎችን በአግባቡ ሰርተው የማቅረብ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህ ስራ ወጣቱን በስፋት ባሳተፈ መልኩ እንደሚከናወን የመንግሥት ድርሻ ብቻ ሳይሆን የወጣቶችቻንንና የሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ፣ ፓኬጆቹ ውስጥ የነበረውን ውስን የወጣቶች ተሳትፎ በማስቀረት ሙሉ በሙሉ ባለቤት የሚሆኑበትና በስፋት የሚሳተፉበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

ወጣቱ የገዢውን ፓርቲና የመንግሥትን የጥልቅ ተሐድሶ እንቅስቃሴ በጥልቀት በመገንዘብ ሀገሩን ለማልማትና ለማሳደግ፤ ሰላሟንም ነቅቶ በመጠበቅ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል፡፡ በተለይም ሀገሪቱ በሕዳሴው ጉዞዋ በፍጥነት እየተራመደችና አዳዲስ ድሎችንም እያስመዘገበች መገኘቷ፤ ያለውም ልማትና እድገት ለወጣቶች ታላቅ ተስፋ መሆኑን ወጣቶች በውል መረዳት አለባቸው፡፡

ወጣቶችን ጨምሮ ከመላው የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚጠበቀውን ያህል ከእድገቱ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ፣ የሥራ አጥነት ችግር በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተፈታ፣ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ለሥርዓቱ አደጋ ሆነው መደቀናቸውን ወጣቶች በውል ተገንዝበው ከመንግስት ጎን በመቆም የበለጠ ለሀገር ልማትና እድገት፣ ችግሮችንም በጋራ ለመፍታት በንቃት መሳተፍ ያለባቸው ጊዜ ቢኖር አሁን ነው፡፡

 

ይነበብ ይግለጡ

Published in አጀንዳ
Thursday, 09 February 2017 18:57

አዋጁ ይተግበር !

ማንኛውም አዋጅ የሚወጣው ለህብረተሰብ ጥቅም መሆኑ ግልፅ ነው ። ለህብረተሰብ ( በተለይ ለብዙሃኑ) የማይጠቅም አዋጅ አይወጣም ። የማይተገበር አዋጅም መውጣት የለበትም።ስለሆነም በማንኛውም መስክ የሚወጡ አዋጆች/ህጎች የወረቀት ላይ ነብር ሆነው መቅረት የለባቸውም። ሳይሸራረፉ መተግበርም ይኖርበታል ።

 በተለይ ባለፉት ሁለትና  አስርት አመታት በሃገራችን  ከወጡት አዋጆች መካከል የማስታወቂያ አዋጅ ቁጥር 749/ 2004 ተጠቃሽ ነው ። «ማስታወቂያ ሕብረተሰቡ በምርት ግብይት ወይም በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እድገት ከፍተኛ ሚና  ስለሚጫወት፤ አገሪቱ በገበያ መር የኢኮኖሚ ሥርዓት የምትመራ ከመሆኑ አንጻር ገበያው ጤናማ በሆነ ውድድር እንዲመራ በማድረግ ረገድ ማስታወቂያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስለሚያደርግ፤ማስታወቂያ በሥርዓት ካልተመራ የሕብረተሰቡን መብትና ጥቅም እንዲሁም የአገርን ገጽታ ሊጎዳ ስለሚችል...» እንደሆነ የአዋጁ አስፈላጊነት ላይ ተጠቅሷል።

ስለሆነም በዚህ አዋጅ ስር የተዘረዘሩት አንቀፆች በሙሉ አስፈፃሚው አካልና ባለድርሻ አካላት ሊፈፅሟቸዉ  እንደሚገባ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነዉ ። በተግባር ግን ይህ ሙሉ ለሙሉ እየሆነ አይደለም።በተለይ ደግሞ የአልኮል መጠጥን ማስታወቂያ በተመለከተ በአዋጁ የተቀመጠው ድንጋጌ እየተተገበረ አይደለም።

በማስታወቂያ አዋጁ  አንቀፅ 26 ንኡስ አንቀፅ 3 ተራ ቁጥር ሀ ላይ «ማንኛውም የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያ የአልኮል መጠጡን መውሰድ ለጤና ተስማሚ እንደሆነ፣ ግላዊ ወይም ማህበራዊ ስኬትን እንደሚያስከትል፣ የተሻለ ሥነ ልቦናዊ ወይም አካላዊ ብቃት እንደሚያስገኝ ወይም ፈዋሽ እንደሆነ የሚገልፅ ወይም በተደጋጋሚ ወይም ከልክ በላይ እንዲጠጣ የሚገፋፋ መሆን የለበትም» ይላል።በተግባር በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡ ማስታወቂያዎች ግን ከዚህ ድንጋጌ የሚፃረሩ ናቸው።ስለዚህ ይህ አካሄድ መለወጥና መስተካከል አለበት።አዋጁም ተፈፃሚ ሊሆን ይገባል።አዋጁን የሚያስፈፅመው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንም ኃላፊነቱም በአግባቡ መወጣት አለበት።

ከትራፊክ አደጋ መንስኤዎች አንዱ ጠጥቶ ማሽከርከር መሆኑ ይታወቃል።ስለሆነም ጠጥቶ ማሽከርከር ትክክል እንዳልሆነ የሚገልፅ ማስታወቂያ በሚያስተላልፍ መገናኛ ብዙሃን በተፃፃሪ ደግሞ መጠጥ መጠጣት መልካም መሆኑን የሚያስረዳ ማስታወቂያ መመልከት የተለመደ ሆኗል ።ይህ እርስ በእርስ የሚጣረስ ማስታወቂያን  ለህብረሰተቡ  ያዉም በቀጥታ ማቅረብ ትክክል አይደለም። በመሰረቱ በየትኛውም መንገድ የአልኮል መጠጥ መጠጣትን በሚያበረታታ መንገድ  ማስተዋወቅ እና ሰዎች በመልካም ጎኑ እንዲያዩት ማድረግ ተገቢ አይደለም።በተለይ ደግሞ ህፃናትን ጨምሮ በሚመለከቱትና በሚሰሙት መገናኛ ብዙሃን መነገሩ ትክክል ስላልሆነ ማስታወቂያዎቹ  በህጉ መሰረት ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል። የማንኛዉም አዋጅ አንዱ  አላማ ህብረተሰቡን ከአደጋ እና ከማህበራዊ ቀወስ መጠበቅ በመሆኑ አስፈፃሚው አካል ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።

አዋጁ ያስፈለገው ማስታወቂያ በህግና በአግባብ ካልተገራ የማህበረሰቡን መብትና ጥቅም እንዲሁም የአገርን ገፅታ ሊጎዳ ስለሚችል ይህንኑ ለመከላከልም  ነው። በእርግጥ ኢትዮጵያ  የአልኮል መጠጥ ፖሊሲ የላትም። ይህም አዋጁ ከአዋጅነት ባለፈ የተፈፃሚነት አቅሙ እንዲቀንስ ያደርገዋል ሲሉ የህግ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።ስለዚህ ፖሊሲ አስፈላጊ ከሆነም ፖለሲ ማውጣትም  ተገቢ ነው።ለግዜው ግን የወጣውን  አዋጅ በሁለንተናዊነት  በመተግበር ጉዳቱን መቀነስ ይገባል።

 የስነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉትም ህብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ያላቸውን ጉዳዮች ከአልኮል መጠጦቹ ጋር በማያያዝ መሰራቱ ከስርአት የወጣና ጤናማ አይደለም። ከወጣትነት፣ ከቁንጅና፣ ከአማላይነት፣ ከበጎ ተግባር፣ ከስኬት፣ ከደስተኛነት ጋር አያይዞ ማስተዋወቁም   አሉታዊ ጎኑ ይበዛል። ምክንያቱም በርካታ ወጣቶች አይረሴ ማስታወቂያዎቹን ስለሚከታተሉ ተጽዕኖ ያድርባቸዋል።ስለዚህ ከስነልቦና አንፃርም አልኮልን ማስተዋወቅ ጉዳት ስላለው በአዋጁ መሰረት ገደብ ሊበጅለት ይገባል የሚለዉን ሃሳብ በአፅንኦት ለመናገር እንደፍራለን ።

በመሰረቱ የአልኮል መጠጦች ከበጎ ነገሮች ጋር ተያይዘው መተዋወቃቸዉ የሚፈጥረዉ ተፅእኖም በሚዛኑ ሊታይ የሚገባዉ ነዉ ። በማህበረሰቡ  ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው ሰዎችና ጉዳዮች፣ታሪካዊና ባህላዊ ክዋኔዎች ከአልኮል መጠጣት ጋር ሲያያዙ የሚፈጠረዉ መደናገር በቀላሉ ሊታይ አይችልም  ። የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያ ድግግሞሽም  መገደብ አለበት ። ካልሆነ ማስታወቂያዎቹ  አልኮል ጠጪነትን በማበረታታት  ቤተሰባዊና  ማህበረሰባዊ ጠንቅ መፍጠራቸዉ ብቻ ሳይሆን የጤና ችግሮች እንዲበረክቱም  በር ይከፍታሉ፡፡  የስራ  ውጤታማነትም  ይቀንሳል ።  ስለዚህ የማስታወቂያ አዋጁ  በአግባቡ ስራ ላይ መዋል  ይኖርበታል ።

በጥቅሉ በሃገራችን በተለያዩ አስፈፃሚ ተቋማት የሚተገበሩና  ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያድረጉ አዋጆች መዉጣታቸዉ  ይበል የሚያሰኝ ነዉ ።እነዚህ አዋጆች ሲወጡ አስፈላጊነታቸው በአስፈፃሚው ተቋምና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም  ታምኖባቸው ነው። ስለሆነም በአግባቡ ተተግብረው ህዝቡን ና ሀገርን ተጠቃሚ ማድረግ አለባቸው። የማይተገበርና የማይጠቅም  ህግ ከሆነ ደግሞ ቀድሞውኑም  መውጣት የለበትም።የወጣ ህግ አለመተግበሩ  ደግሞ  እንደሌለ ስለሚቆጠር  ወይም መሻር ይኖርበታል ።ስለዚህ የማስታወቂያ አዋጁን በመተግበር በአልኮል ማስታወቂያዎች ላይ ገደብ መጣል  ለነገ የማይባል ተግባር ሊሆን ይገባል ።

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።