Items filtered by date: Tuesday, 01 August 2017

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የማህበራት ማደራጃና እውቅና ዳይሬክቶሬት ከተማ አቀፍ እውቅና ከሰጣቸው የስፖርት ማህበራት መካከል የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አንዱ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ የተሰጠውን እውቅና መሰረት አድርጎ በከተማዋ ውስጥ እግር ኳስ ስፖርት ተመራጭና ተዘውታሪ እንዲሆን የማድረግና ታዳጊ ስፖርተኞችን የማፍራትና የማብቃት ሃላፊነት ተስጥቶታል።

   በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ ከተማዋን የሚወክሉ ብቃት ያላቸው ተወዳዳሪዎች የማፍራትና ለክለቦቹ ሙያዊም ሆነ ቁሳዊ ድጋፍ ማድረግም ከተጣለበት ሃላፊነቶች መካከል ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። ለዚህ ሃላፊነቱ ተግባራዊነትም፤በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ክለቦች መካከል በየዓመቱ የከፍተኛና የአንደኛ ዲቪዚዮን የሴቶችና የታዳጊ ወጣቶች ውድድሮች ያዘጋጃል። ከዚህ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጋር በመተባበር በዓመት አንድ ጊዜ የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫን ያስተናግዳል።

  አዲስ ዘመንም የፌዴሬሽኑን የዘንድሮ ዓመት ውድድሮች አተገባበር በሚመለከት ከስራ አስፈፀሚና የውድድርና ስነ ስርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢው ከአቶ በለጠ ዘውዴ ጋር ቆይታ አድርጓል።

   አዲስ ዘመን፡- ፌዴሬሽኑ የእግር ኳስ ስፖርት በከተማዋ ተመራጭና ተዘውታሪ እንዲሆን የክለቦችን ተሳታፊነት በማሳዳግ ረገድ ሃላፊነቱን እንዴት ተወጥቷል?

    በአቶ በለጠ፡- ፌዴሬሽኑ በከተማዋ ውስጥ እግር ኳስ ስፖርት ተመራጭና ተዘውታሪ እንዲሆን ለማድረግና ታዳጊ ስፖርተኞችን ለማፍራትና ለማብቃት ለተጫዋቾች የውድድር ዕድል ለመፍጠር በየዓመቱ የውስጥ ውድድር ያደርጋል። በዚህም በተለይ ክፍለ ከተሞች በስፖርቱ እንዲሳተፉ በማድረግ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ጥረቶች በማድረግ ውጤታማ ተግባርም መፈፀም ተችሏል። በአሁኑ ወቅት ከአንድ ክፍለ ከተማ ማለትም ከኮልፌ ክፍለ ከተማ በስተቀር አብዛኞቹ ብሄራዊ ሊግና በከፍተኛ ሊግ በወንድም በሴትም እየተካፈሉ ናቸው። ከዚህ በተጓዳኝ በርካታ የግል ክለቦች ወደ ውድድሩ እንዲመጡ ማድረግ ችለናል።

   አዲስ ዘመን፡- ፌዴሬሽኑ ቡድኖችን በመደገፍ ተተኪዎችን በማፍራት ረገድ ውስንነት እንዳለበት በዘርፉ ባለሙያዎችና ክለቦች ሲወቀስ ይሰማል፣ ይህን ምን ያህል ይስማሙበታል?

  አቶ በለጠ፡- ወቀሳው ትክክል ነው። ፌዴሬሽኑ ክለቦችን በተለያዩ መንገዶች የመደገፍ ሃላፊነት አለበት። ይሁንና በዚህ ረገድ የሰራቸው ሥራዎች ብዙም አይደሉም ለማለት እደፍራለሁ። ለክለቦቹ ሙያዊም ሆነ ቁሳዊ ድጋፍ በማድረግም ረገድ ፌዴሬሽኑ ደግፏል ብዬ አላስብም። ከተማዋን የሚወክሉ ክለቦች ወደ ክልል ሻምፒዮና ሲሄዱ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ለሚወጡት መጠነኛ ድጋፍ በማድረግ ከመሸኘት በስተቀር በድጋፍ ደረጃ የሰራነው የለም። ይህም የሆነበት ምክንያት ፌዴሬሽኑ ክለቦች በበጀት እንዲጠናከሩ የማድረግ ስራ በብዛት ያለመስራቱም ጭምር ነው። በየዓመቱ የምናካሂዳቸውን ውድድሮች ስፖንሰር በመፈለግ ክለቦቹ የሚጠናከሩበትን አሰራር በመቅረፅ ረገድ ስራዎች አልተሰራም። ይህን ባለመስራታችንም በባለፈው ዓመት የተቋቋሙ ክለቦች ዘንድሮ ሲፈርሱ እናያለን።

     እርግጥም ተተኪዎችን የማፍራት ችግር አለ። ይህም ምንም የማይካድ ነው። ባለፈው ዓመት 16 እና 12 ቡድን ተመዝግቦ ዘንድሮ ወደ ስምንትና ሰባት ከወረደ ተተኪዎች የማፍራት ችግር እንዳለብን የሚያሳይ ነው። ተተኪዎች የምናመጣበት መንገድ በራሱ ትክክል አይደለም። ታዳጊና ወጣቶች በስፖንሰር እንዲደገፉ ማድረግ የእኛ ስራ ነው። ታዳጊና ወጣቶች መጨረሻው ዓመት ላይ፤ቢያንስ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የወጡትን ወይ በገንዝብ አሊያም በቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ይኖርብናል። ይህ ሲሆን ታዳጊና ወጣቶች ይመጣሉ።

   ሲፈርሱ ለምን ፈረሱ ብለን የምንገመግምበት ሂደት መኖር አለበት። በደጋፊ ማነስ ነው ወይንስ፤ በራሳችሁ ነው ብለን  የክለቦችን አመራር የማናገር ባህል የለንም። አንድ ቡድን ፈረሰ ፈረሰ ነው። የመመዝገቢያ ገንዘብ ከሆነ ችግሩ ይህን የምናግዝበት ሁኔታ መፈጠር አለበት።

   አዲስ ዘመን፡- በውድድሮቹ ላይ የሚስተዋለው የእድሜው ጉዳይ ተተኪዎቹን የማፍራት ሂደቱ ላይ የፈጠረው ጫና ይኖር ይሆን?

   አቶ በለጠ፡- በእርግጥም አንዳንድ አሰልጣኞች ተተኪን ለማፍራት ሳይሆን ትኩረት የሚያደርጉት ለውጤትና ውጤት ብቻ ነው። እኛ እየታዘብን ያለነውም ይህን ነው። በተተኪዎች ላይ ሰርተው ቢመጡ ውጤታማ እንደሚሆኑ አያውቁትም። አያምኑምም። ብዙ ጊዜ ከክለቦቹ የመገናኘት አጋጣሚው አለኝ። ታዳጊና ወጣት ይዘው የሚመጡ አሰልጣኞች ምንም ጥቅም አያገኙም።

  ይህ ምን ማለት ነው ለምሳሌ፤ባለፈው ዓመት አንድ ታዳጊና ወጣት ቡድን ይዞ የመጣ አሰልጣኝ ወይ በኒያላ በመብራት ሃይል አሊያም በመድን ወይም ሌላ ክለብ አምስትና ስድስት ተጫዋቾች ይወሰድበታል ። ተጫዋቾቹ ሲሄዱ ግን አሰልጣኙም ሆነ ክለቡ የሚያገኙት ጥቅም የለም።

   ክለቡ አሊያም አሰልጣኙ ለዓመታት የለፋባቸውን ተጫዋቾች ሌሎች ሲወስዱበት ቢያንስ ድጋፍ የሚያገኝበት መንገድ በመቀየስ ረገድ የተዘረጋ ነገር የለም። ይህ ችግርም ታዳጊ ቡድኖች እንዳይመጡና አሰልጣኞችም በታዳጊዎች ላይ መስራትን እንዳይመርጡና ተስፋ እንዲቆርጡ እያደረገ ነው። በመሆኑም የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከእነዚህ ክለቦች ጋር በመሆን ክለቦቹ የሚያፈራቸው ልጆች ወደ ትልልቅ ክለቦች ሲሄዱ ጥቅም የሚያገኙበትን መስመር መዘርጋት አለበት። ክክለቦቹ ጋር በመነጋገር አንድ ደንብና መመሪያና ማዘጋጀት የግድ ይለዋል።

  አዲስ ዘመን፡- ፌዴሬሽኑ በየዓመቱ የከፍተኛና የአንደኛ ዲቪዚዮን የሴቶችና የታዳጊ ወጣቶች ውድድሮች ያዘጋጃል፣የዘንድሮው ውድድር እንዴት ይቃኛል?

  አቶ በለጠ፡- ፌዴሬሽኑ በከተማዋ የሚስተዋለውን የተተኪ እግር ኳስ ተጫዋቾች ችግር ለመቅረፍ እና ለተጫዋቾች የውድድር ዕድል ለመፍጠር በየዓመቱ የውስጥ ውድድር ያካሂዳል። ምንም እንኳን የዘንድሮው ውድድር ከባለፉት ዓመት በተሳታፊዎች ቁጥሩ ቢቀንስም፤ክለቦችም በእጅጉ ተዘጋጅተው የተወዳደሩበት፤ አስደሳችና እስከመጨረሻዋ ቀን ድረስ በነጥብ ተቀራራቢ ክለቦች የተሳተፉበት ነው። ውጤታቸው የተቀራረበ በመሆኑ በጎል ለመለየት እስገመገደድ ደርሰናል። እኛም ውድድሮቹ በህግና ደንብ እንዲመሩ ከማድረግ በስነምግባር የታነፀ ስፖርተኛ ከማፍራት አንፃር እንደ ውድድርና ስነ ስርዓት ኮሚቴ ብዙ ርቀቶች ሄደናል። ውድድሩንም በቅርበት ተከታትለነዋል።

  ይህን ስንል ግን ችግሮች የሉም ማለት አይደለም። በዘንድሮ ዓመት የገጠመን ፈተና በጣም ከባድ ነው። ከአቅምና ውጤት ጋር ተያይዞ ያቋረጡ ቡድኖች ገጥመውናል። በዓመት አንድ ጊዜ ካልሆነ በስተቀር የምናወጣቸው ደንቦች በደንብ ግንዛቤ ፈጥረን በየጊዜው ለክለቦቻችን ማሳወቁ ላይ እጥረቶች ነበሩብን። ይህ ባለመሆኑ የገጠሙን ችግሮችም አሉ።

  የዘንድሮው ውድድር ከባለፉት ዓመት በተሳታፊዎች ቁጥሩ ቀንሷል። ባለፈው ዓመት ወጣት 16 ታዳጊ 12 ቡድኖች የተሳተፉ ሲሆን ዘንድሮ 8 ወጣት 7 ታዳጊ ብቻ ነው። የክለቦች ተሳትፎ የቀነሰበት ትልቅ ምክንያት ፌዴሬሽኑ የምዝገባ ገንዘብ ማሻሻሉና መጨመሩ ነው። ይህም  ክለቦች የመመዝገቢያ ክፍያ እጥረት እንዲያጋጥማቸውና ከውድድር ውጪ እንዲሆኑ የተሳታፊዎቹ ቁጥር እንዲቀንስ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።

  ከዚህ በተጓዳኝ የእድሜ ጉዳይ አለ። እኛ እድሜ የምናጣራው እንደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በምርመራ አይደለም። በእይታ ነው። ይህ እንደመሆኑ ልትሳሳት ትችላለህ። በጣም እድሜያቸው ከፍ ያሉ ተጫዋቾችን ይዘው በመቅረባቸው ምክንያት በርካታ ክለቦች ብዙ ልጆች ይወድቁባቸዋል። አሰልጣኞች ቀድመው ልጆችን አዘጋጀተው የመምጣት ነገር የለም። ይህ በቀጣይ አንድ መፍትሄ የሚያሻው ጉዳይ ነው።

  አዲስ ዘመን፡- በዘንድሮው ውድድር ለክለቦች ከፍተኛ ራስ ምታት ከሆኑ ችግሮች ቀዳሚው የሆነውን የሜዳ ችግር እንዴት ይገልፁታል?

   አቶ በለጠ፡- ዘንድሮ የአበበ ቢቂላ ስታዲየም መዘጋት ጨዋታዎችን በጃን ሜዳ እንድናካሂድና ከባድ ፈተና እንዲገጥመን ምክንያት ሆኗል። ጃንሜዳ ለተጫዋቾች ምቹ አይደለም። ለጉዳት የሚያጋልጥ ነው። ሜዳው በተለይ ለሴቶች እጅግ ፈተና ነው። ልብስ መቀየሪያ ቦታ እንኳን ማግኘት አይችሉም። ሴቶች የሚቀይሩበት ቦታ እያጡ ሲቸገሩ ይታያል። ሰርቪስ ያለው ምናልባት እዛው ውስጥ ሊቀይር ይችላል። ይህን ስታይ በእጀጉ ታዝናለህ።

   በሜዳዎቻችን ለውድድር አመቺ ያለመሆን ምክንያት ተመልካችና ተጫዋቾቹ የማይለዩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ተጫዋቾች ለቅጣት የሚዳረጉት፤ተመልካችና ተጫዋቹን መለየት ስላልተቻለ ነው። አራተኛ ዳኛና ኮሚሽነሩም፤ በተመልካች ተውጠው እያጣናቸው እንቸገራለን። ሜዳው ትልቅ ስለሆነ ለታዳጊዎች አይመችም። ለታዳጊዎች የሚሆን ሜዳ የለም።

  አዲስ ዘመን፡- የዳኞች ችግርንስ?

  አቶ በለጠ፡- የዳኞች ጉዳይ የራሱ ኮሚቴ አለው። ይሁንና እንደ ውድድርና ስነ ስርዓት ጥራት ያለው ዳኛ እንዲመደብልን እንፈልጋለን። ውድድራችን በሰላም ተጀምረው በሰላም እንዲያልቁ እንፈልጋለን። ፌዴሬሽኑ በርካታ ዳኞችን እያወጣ ነው። የዳኞች ችግር የለበትም። ይሁንና አንዳንድ ዳኞች ቦታ ይመርጣሉ። አበበ ቢቂላ ማጫወትና ጃን ሜዳ ማጫወት ልዩነት አለው። አብዛኞቹ ዳኞቻችን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጨዋታዎች ይያዛሉ። ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቅድሚያ የሚሉት አለ።

  የዳኞች ክፍያ ሌላኛውና ትልቁ ችግር ነው። ዳኞች በሚፈለገው መልኩ መጥተው እንዳያጫውቱ የሚያደርገው የክፍያው ሁኔታ ነው። ክፍያው የተሻለ በመሆኑ የግል ውድድር ማወዳደር ይመርጣሉ። ዳኞቻችን የውጭ ውድድሮች እያወዳደሩ ማለትም ባይሆን ለራስ ቅድሚያ ቢሰጡ የተሻለ ነው። ዳኞችን በማብቃት ረገድ፤ተከታታይ ስልጠና የመስጠት ችግርም አለብን። ባለፈው ዓመት አንድ ድርጅት መቶ ዳኞችን ለማሰልጠን ጥያቄ ቢያቀርብም ተፈፃሚ አልሆነም።

   ዳኞች ቢመደቡም እንኳን እንደ ጃንሜዳ በመሳሰሉ ቦታዎች የዳኞች የልብስ መቀየሪያና ማስቀመጫ የለም። ከፍለው ካልሆነ ሻወር የሚወስዱበት ቦታ እንኳን የለም። እንደ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አይደለም። ትጥቅና ንብረታቸውን የሚያስቀምጡት ሜዳ ላይ ነው። ይወሰድባቸዋል። ይህ በራሱ ትልቅ ችግር ነው። ውድድሩን ያማረና የደመቀ ለማድረግ መሰል ችግሮች ቅድሚያ ማስተካከል  ያስፈልጋል። ለዚህም ከወጣቶችና ስፖርት እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ይበልጥ መነጋገር የግድ ይላል።

  አዲስ ዘመን፡- ዘንድሮም ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች የሚያፈሩ ቡድኖች እምብዛም አልተመለከትንም፤ ለሴት ቡድኖች እጥረት መንስኤና መፍትሄ የሚሉት ምን ይሆን?

  አቶ በለጠ፡- ፌዴሬሽኑ የሚያደርገው ተጨማሪ ድጋፍ እንዳለ ሆኖ በሴቶች ደረጃ ክለብ አቋቁሞ የማምጣት ክፍተኛ ችግር አለ። የግል ክለቦችና አሰልጣኞች በራሳቸው በየሰፈሩ የያዛቸው ካልሆኑ በስተቀር ክፍለ ከተሞች ያላቸው ተሳትፎ በጣም ደካማ ነው። ክለብ ያላቸው ክፍለ ከተሞች በጣም አነስተኛ ናቸው።

  ምንም እንኳን የዘንድሮው ውድድር ተሳታፊዎች ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ምንም ልዩነት ባያሳይም፤ ውጤታማነቱም ፉክክሩም በጣም አነስተኛ ነው። የዘንድሮው ውድድር የተጠናቀቀው በአካዳሚና በቂርቆስ የበላይነት ነው። ቀሪዎቹ ስድስት ቡድኖች የትራንስፖርት እንኳን የላቸውም። ትጥቅ አሟልተው አይመጡም። ምግብ አያገኙም። ከውሃ አንፃር እንኳን የሚያገኙት አልነበረም።

  ለአብነት በዚህ ዓመት ጉለሌ፤ አራዳ፣ የካ፤ተሳትፈዋል። ልጆቹ ስሙን ይዘው ይሳተፉ እንጂ አንድም የተደረገላቸው ድጋፍ የለም።የመመዝገቢያ ክፍያውን የሸፈኑት እንኳን የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ አቃቤ ነዋይ የሆኑት ኢንጂነር ሃይለእየሱስ ፍስሃ ናቸው። ይህ ባይሆን እነዚህም ክለቦች የመወዳደር ሁኔታ አይታሰብም ነበር።

  ሴቶች ላይ በጣም መስራት አለብን። የወጣቶችና ስፖርትም በዚህ ረገድ ሊያግዘን ይገባል። የሴቶች ቡድን የሌላቸው ክፍለ ከተሞች፤ቡድን እንዲያቋቁሙ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው። ለዚህም አስፈላጊው ህግና መመሪያ መተግበር አለበት። የማስገደዱ ነገር እንዳይኖር ደግሞ አብዛኞቹ የግል ክለቦች ናቸው። እነዚህን ክለቦች ሴት እንዲይዙ ማስገደድ ይቸግረናል። ወንዶችን ለመያዝም እየተንገዳገዱ ነው። ይሁንና የሌላቸውን ክፍለ ከተሞችን ብናስገድድ በዚህም ውጤታማ እንሆናለን ችግሩን ማስወገድ እንችላለን ብዬ እምናለሁ። ይህ ካልሆነ ለመላ ኢትዮጵያ እንኳን የምናሳትፋቸው ልጆች  እናጣለን ብዬ አስባለሁ።

   አዲስ ዘመን፡-በአገር አቀፍ የክልል ክለቦች ሻምፒዮና የአዲስ አበባ ከተማ ውጤት እየራቀው ነው ዘንድሮስ በውጤት ደረጃ ምን ይጠበቃል?

  አቶ በለጠ፡- በ2006 በአዋሳ የተካሄደው ሻምፒዮና የተጠናቀቀው በአዲስ አበባ የበላይነት ነው። የካ ሻምፒዮን ከሆነበት ከዚህ ውድድር ወዲህ ግን በውጤት ደረጃ ድክመቶች ታይተዋል። ላለፉት ዓመታት በሌሎች ክልሎች ተበልጠናል። ዘንድሮ ግን ከአንደኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፣ጉለሌ ክፍለ ከተማ፣መርካቶ አካባቢ እና ናኖ ሆርቦ ቡድኖች አዲስ አበባን በመወከል በአገር አቀፍ የክልሎች ሻምፒዮና ላይ ጠንካራ ተወዳዳሪ በመሆን የተሻለ ውጤት እንደሚያመጡ አምናለሁ። ለዚህም በቂ ዝግጅት አድርገናል።

  አዲስ ዘመን፡- የፌዴሬሽኑ ትኩረት ለክልል ክለቦች ሻምፒዮን ከተማዋን የሚወክላት ክለብ ማፍራት ላይ ብቻ ነው የሚባለውስ?

  አቶ በለጠ፡- ይህን ካነሳን በጣም ከባድ ነው። የእኛ የመጨረሻ ግባቸው ይመስለኛል። ግን አይደለም። ብሄራዊ ሊግ ላይ የሚገኙ ክለቦችን እንኳን ሰብስበን አናውቅም። ለአብነት ዘንድሮ የካ ከፍተኛ ሊግ ገብቷል። የካ ከፍተኛ ሊግ መግባት የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ይመለከተዋል። ችግራቸውንም ይሁን ሌሎች ጉዳዮች አዋይተናቸው አናውቅም። ይህ ትልቅ ክፍተት ነው።

  ይሁንና ክለቦች ፕሪሚየር ሊግ ሲገቡ የፌዴሬሽኑ ተሳትፎ ውስን ይሆናል። በክለቡ ቦርድ ውስጥ እንኳን ውክልና ሊኖረው ይገባል። የእኛ መብትና ባለቤትነት ምንድነው ብለን እንኳን መጠየቅ አልቻልንም።ይህ ሊስተካከል ይገባል።

  እኛ የምንሰራው ክ/ከተማዋን የሚወክል ክለብ ለፕሪሚየር ሊጉም ሆነ በሌሎች መድረኮች ለማበርከት ነው። ትኩረታቸው ለክልል ክለቦች ሻምፒዮና ለመሳተፍ ብቻ ነው የሚባለው ሃቅ ነው። ዓመታዊ ስራችንን እንገምግም ብለን ብንቀመጥ የሚበዛው የውድድሩ ነው። ፌዴሬሽኑ ዘንድሮ 77 ቡድኖች አወዳደረ። አራትና አምስት ክለቦች በክክል ክለቦች ሻምፒዮና ላከ። ይህ አይደለም ግባችን። ግቡ ሊሆን የሚገባው እነዚህን የሚተካ ሌላ ማምጣት ላይ ነው። የእኛ የመጨረሻ እሳቤ ውድድር ጨረስን ላክንም በሚቀጥለው ዓመት የገባው ይገባል። የወደቀው መልሶ ይወዳደራል። ይህ መሆን የለበትም።  ከክልል ክለቦች ሻምፒዮናውን ተሻግረው ወደ ሊጉ መግባት  የቻሉ ክለቦችን በሙያም ሆነ በሌሎች አስተዋፅኦዎች ተከታትሎ መደገፍ ይኖርብናል።

አዲስ ዘመን፤የዘንድሮው ሲቲ ካፕ የውድድር መርሃ ግብር ከፕሪሚየር ሊጉ ጅማሮ ጋር ይጋጫል፤ይህን አስባችሁበታል?

   አቶ በለጠ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ዳይሬክተሮች በኩል ስልክ ተደውሎ መስከረም 28 እና 29 የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር እንደሚካሄድና ጥቅምት አራት ደግሞ ፕሪሚየር ሊጉ  እንደሚጀመር ተነግሮኛል። እኔም ለሚመለከተው አካል አሳውቄ አለሁ።

   የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደግሞ በተለምዶው የሲቲ ካፕ ውድድሩን የሚያካሂደው ከመስከረም 25  እስከ ጥቅምት15 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። የፌዴሬሽኑ ገቢም በዓመት አንድ ጊዜ በሚያካሂደው በዚሁ የሲቲ ካፕ ውድድር ላይ  ዋነኛ መሰረቱን ያቆመ ነው። ፌዴሬሽኑ በራሱ በጀት የሚንቀሳቀስ ነው። ከመንግስት የሚያገኘው በጀት የለም። በፊት የሚደረግለት ድጎማ አሁን ቀርቷል። ይህ ገቢ ቢቋረጥ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ቆመ ማለት ነው።ይህ ለእኛ እጅግ አደጋ ነው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥቅምት አራት ካካሄደ እኛ መቼ ውድድር ልናካሂድ ነው? ይህ መታሰብ ያለበት ይመስለኛል።

  አዲስ ዘመን፡- ይህ ከሆነ እናንተ የውድድራችሁን መርሃ ግብር ለምን አላስተካ ከላችሁም?

   አቶ በለጠ፡- ይህን ማድረግ አይችልም። ምክንያቱ ደግሞ የአየሩ ሁኔታ ነው። እንደሚታወቀው መሰከረም የዝናብ ወቅት ነው። ሰው ከፍሎ ገብቶ ውድድር መቋረጥ የለበትም። ሜዳዎች አይደርቁም። ሳሩ የሚታጨድበት ወቅት ነው። በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንዳናካሂድም እድሳት ላይ ነው።

  ከአየር በተጓዷኝ መስከረም ለፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የእረፍት ወቅታቸው ነው። ቅድመ ልምምድ የሚሰሩበት ወቅት ነው። ጥቅምት ውስጥ ማካሄዳችንም ብዙ ጠቀሜታ አለው። ክለቦችም ብዙ ተዘጋጅተው  እንዲመጡና ለሊጉ ጅማሮ የቀረበ እንደመሆኑ ራሳቸውን የሚፈትሹበት አጋጣሚ ይፈጥራል።

  አዲስ ዘመን፡- የውድድር መርሃ ግብሩን ስታዘጋጁ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ትነጋገራላችሁ? ዘንድሮ ፌዴሬሽኑ በውሳኔው ቢፀና ውድድሩ ሳይካሄድ ይቀራል ማለት ነው?

  አቶ በለጠ፡- እነርሱ ፕሮግራም ያወጣሉ። ይህ ከሆነ በኋላ እኛ በደብዳቤ ፅፈን ቀናችሁን አሸጋሽጉልን የመባባል ነው ያለው። በየዓመቱ መነጋገር አያስፈልግም። በዚህ መልኩ ሳይካሄድ የቀረበት ጊዜ የለም። እስካሁን አጋጥሞኝ አያውቅም። ባለፈው ዓመት በዛ ችግር ውስጥ ሆነን እንኳን ውድድሩን አዘጋጅተናል። ውድድር ማካሄድ ብቻም ሳይሆን ከውጭ ክለብ ለመጋበዝ ጥረት አድርገናል። በእርግጥ በ2008 ውድድር ዓመትም ውድድሩን ወደዚህ አምጥቶብን ነበር። በመነጋገርና በመወያየት ለጉዳዩ እልባት ስጥተናል።

  ሲቲ ካፕ የፌዴሬሽኑ ትልቅ ገቢ ነው። ይህን ገቢ ማግኘት ካልተቻለ ክለቦቻችን ላይ ጫና ይፈጥራል። ይህን ውድድር አላካሄድንም ማለትም በቀጣይ ዓመት የሚከናወኑ ተግባራት ይቀንሳሉ ማለት ነው። በመሆኑም የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ራሱን ችሎ እንዲቆም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ማገዝ አለበት። ይህ ጉዳይ የእኛ ብቻም ሳይሆን የወጣቶችን ስፖርትም ጭምር ነው። ፌዴሬሽኑ የሚጠናከረው በዚህ ገቢ በመሆኑ ቢሮው በዚህ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ የማገዝ ግዴታ አለበት።

  ፌዴሬሽኑም ውድድሩን መግፋት አለበት። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በእርግጠኝነት ይገፋሉ ብዬ አስባለሁ። ሁላችንም የምንሰራው ለስፖርቱ ነው። ክልሎች ደግሞ የራሳቸውን  ገቢ ለማጠናከር እና ስፖርቱን ለማስፋፋት ገቢ ያስፈልጋቸዋል። እኛም ብቻ አይደለንም የምናካሂደው። ደቡብም ያካሂዳል። ደቡብም ሲቲ ካፕ ውድድር አለ። ቢያንስ  እስከ ጥቅምት15 ድረስ ያለውን ጊዜ ለክልሎች መተው አለበት።

  አዲስ ዘመን፡- ስፖርታዊ ውድድሮች በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲቆሙ ከስፖርተኞቹ ጥረት በስተጀርባ ጠንካራ የገንዘብ አቅም ወሳኝ መሆኑ እሙን ነው፤ውድድሮችን የመሸጥና ስፖንሰሮችን የማፈላለግ አቅምና አቋማችሁስ?

   አቶ በለጠ፡- በዓመቱ መጀመሪያ የሚካሄደው የሲቲ ካፕ ውድድር የከተማው ዋንጫ ላይ ከምናገኘው ገቢና ከምናገኘው ስፖንሰር ውጪ በዚህ ደረጃ የምንሄድባቸው ርቀቶች የሉም። የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መስራት አለበት ብዬ የማምነውም ውድድሮችን መሸጥና ስፖንሰሮችን ማፍራት ላይ ነው። ይሁንና ፌዴሬሽኑም ክለቦችም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር ለመዘርጋት የሄድንበት ርቀት የለም። ውስንነት አለበት። ይህን ችግር ለማስወገድ በፌዴሬሽኑ ውስጥ የተቋቋመ ኮሚቴ አለ። የስፖንሰር ሺፕ ኮሚቴ ይሰኛል። ይህ ኮሚቴ ስራውን በአግባቡ መስራት አለበት። እኛ አለመስራታችንና የድርጅቶችን በር ለማነኳኳት ካለመሄዳችን በስተቀር፤ በርካታ ድርጅቶችም ይህን ውድድር ይፈልጋሉ። ሄደን እምቢ ያለን አካል የለም።

   ውድድሩን በመሸጥ የተሳትፎ ክፍያን እንኳን ማስቀረት ይቻላል። ቢያንስ ክፍያው ይቀንስላቸዋል። በእርግጠኝነት በርካታ ክለቦች ይመዘገባሉ። ታዳጊ ወጣቶች ማምጣትና ተተኪዎች መፍራት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ አመስግናለሁ።

አቶ በለጠ ፡- እኔም እመሰግናለሁ።

Published in ስፖርት

በደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ሀዲያ ዞን በሌሞ ወረዳ ተወልደው ያደጉት አቶ ገዛኸኝ ሳሙኤል ነዋሪነታቸው በሆሳዕና ከተማ ነው፡፡ ግለሰቡ ከ1983 እስከ 1999 ዓ.ም ለአስራ ስድስት ዓመታት በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች በሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመምህርነት አገልግለዋል፡፡

በ1999 ዓ.ም ወረዳው ለመምህሩ የትምህርት እድል ይሰጣቸዋል፡፡ የተሰጣቸውን የትምህርት እድል ተጠቅመው የነበራቸውን የትምህርት ደረጃ ከዲፕሎማ ወደ ዲግሪ ለማሻሻል በመደበኛው የትምህርት ፕሮግራም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያመራሉ፡፡ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ይቆዩና በስነ ትምህርት ኮሌጅ ውስጥ ታሪክ እና ስነ- ዜጋ ትምህርት አጥንተው በ2001 ዓ.ም አጠናቅቀዋል፡፡ ከፍተኛ ውጤት (3 ነጥብ 7) በማስመዝገብም በሀምሌ 17 ቀን 2001 ዓ.ም በማዕረግ ተመርቀዋል፡፡

ቅሬታ ለቀረበበት ምክንያት የሆነው ጉዳይ የተከሰተው በ2001 ዓ.ም ነው። በሐምሌ 24 ቀን 2001 ዓ.ም (በተመረቁ በአንድ ሳምንት) ወደ ወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ተመልሰዋል፡፡ ለጽህፈት ቤቱ ትምህርታቸውን ስለጨረሱ እና ያስተምሩ የነበሩበት ሌሞ ወረዳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስለሌለ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ተገቢውን ምደባ እንዲሰጣቸው የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት የድጋፍ ደብዳቤ እንዲጽፍላቸው ያመለክታሉ፡፡

የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊም ጥያቄያቸው ታይቶ ምላሽ እንዲሰጣቸው መርተዋል፡፡ ሆኖም ጉዳዩን አይቶ ምላሽ እንዲሰጥ የታዘዘው የጽህፈት ቤቱ የቅሬታና ይግባኝ ሰሚ ዋና የስራ ሂደትም ሆነ ወረዳው ለማመልከቻቸው ምላሽ ሳይሰጥ ወራት እንደተቆጠሩ መምህር ገዛኸኝ ያወሳሉ ፡፡

ለጽህፈት ቤቱ ያስገቡት ማመልከቻ የጽሁፍ ምላሽ ሳያገኝ ቀናት እያለፉ ተተኩ፡፡ ወራትም አልፈው ወራት ተተኩ፡፡ ለጽህፈት ቤቱ ያስገቡት ማመልከቻ የውሃ ሽታ ሆኖ ሲቀር ቅሬታቸውን ለዞኑ ትምህርት መምሪያ በአካልና በጽሁፍ ከአንዴም ሶስቴ አቅርበዋል፡፡ ያስተምሩ የነበሩበት ወረዳ ውስጥ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ስለሌሉ የትምህርት ውጤት እና የአገልግሎት ዘመን ከግንዛቤ በማስገባት መምሪያው ምደባ እንዲሰጣቸው አመልክተዋል፡፡ መምሪያው ግን ምንም አይነት ምላሽ በጽሁፍ አለመስጠቱን ተናግረዋል፡፡

ከወረዳው ጽህፈት ቤትም ይሁን ከዞኑ ትምህርት መምሪያ ምንም ምላሽ አለመሰጠቱ ያሳሰባቸው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ክፍት ቦታ እስኪገኝ፤ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመሄዳቸው በፊት ይሰሩ የነበሩበት ማስቢራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመመለስ ላይ ታች በሚሉበት ወቅት ከወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት የደረሳቸው ደብዳቤ በጣም አስደንጋጭ ነበር፡፡ ደብዳቤውም ዱባንቾ በሚባል የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ተቀጥረው በስራ ገበታ ላይ ስላልተገኙ እና ተደጋጋሚ ማስታወቂያ ወጥቶ ቀርበው ባለማመልከታቸው ከስራ መሰናበታቸውን የሚያስረዳ ነበር፡፡

አቶ ገዛኸኝ እንደሚሉት ምደባ እያላቸው እና ለዘመናት ይሰሩ የነበሩበት የማስቢራ  ትምህርት ቤት በስራ ገበታ ላይ ስላለመገኘታቸው ምንም አይነት ማስታወቂያም አላወጣም፤ ከስራም አላገዳቸውም፡፡ የስራ ስንብት ደብዳቤም ከማስቢራ ትምህርት ቤት አልሰጣቸውም፡፡ ከስራቸው መታገድ ካለባቸውም መታገድ የነበረባቸው ቀድሞ ያስተምሩ በነበሩበት ትምህርት ቤት ነው፡፡ መምህሩ የታገዱት ግን ስለመመደባቸውም እንኳን ከማያውቁበት ከዱባንቾ ትምህርት ቤት ውስጥ መሆኑ ግራ የሚያጋባ መሆኑን ነው የሚያነሱት፡፡

ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ለሆኑት እና ብቸኛ መተዳደሪያቸው የመንግስት ደሞዝ ለሆናቸው ለመምህር ገዛኸኝ የስራ መታገድ ደብዳቤ መርዶ የተረዱ ያህል አስደንጋጭ ነበር፡፡ አቶ ገዛኸኝ እንደሚሉት ባጋጠማቸው ውስብስብ ችግር ምክንያት ትዳራቸውም ፈርሷል፡፡ ከእናት አባት ጋር ማደግ የነበረባቸው ልጆችም አባታቸው ከስራ መሰናበታቸውን ተከትሎ በቤተሰብ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ከእናት አባት ጋር የመኖር መብታቸውን ተነፍገዋል፡፡

መምህሩ ቅሬታቸውን ከማሰማት አልቦዘኑም፤ ጥያቄያቸውን ለሚመለከታቸው ተቋማት ማቅረባቸውን ተያይዘውታል፡፡ ለዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት፣ ለዞን መምህራን ማህበር፣ ለክልል መምህራን ማህበር፣ ለክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ ለክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስ እና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ እንዲሁም ለርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት አለፍ ሲልም ለፌዴራል እንባ ጠባቂ ተቋም፣ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንዲሁም ለትምህርት ሚኒስቴር ያቀረቡበትን ደብዳቤዎች ኮፒ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አቅርበዋል፡፡

መምህሩ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት አብዛኞቹ ተቋማት ለዞኑ ትምህርት መምሪያ ‹‹ለመምህሩ በዞኑ በሚገኙ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገቢው ምደባ እንዲሰጠው›› በማለት ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ ከእነዚህ ደብዳቤዎች መካከልም ለአብነት ያህል የዞኑ መምህራን ማህበር ጥቅምት 3 ቀን 2002 ዓ.ም  እንዲሁም የክልሉ መምህራን ማህበር ታህሳስ9 ቀን 2002 ዓ.ም ለዞኑ ትምህርት መምሪያ ‹‹መምህራን ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ የሚደረገው የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት በመቅረፍ ለትምህርት ስኬታማነት አስፈላጊውን ሁኔታዎችን በማመቻቸት ተማሪዎች አስፈላጊውን ትምህርት እንዲያገኙ ለማድረግ በመሆኑም መምህሩ ተገቢው ምደባ እንዲሰጠው›› በማለት ደብዳቤ ጽፏል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለዞኑ ትምህርት መምሪያ መስከረም 8 ቀን 2002 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ ‹‹መምህሩ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲመደቡ እና ጥቅማ ጥቅማቸው እንዲከበር›› በማለት መመሪያ ሰጥቷል፡፡ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት የአስተዳደራዊ ቅሬታና አቤቱታ ጉዳዮች ውሳኔ አሰጣጥ ዋና የስራ ሂደት በጥቅምት7 ቀን2002 ዓ.ም ለዞኑ ትምህርት መምሪያ በጻፈው ደብዳቤ ‹‹የክልሉ ትምህርት ቢሮ የሰጠው መመሪያ ተግባራዊ እንዲደረግ እንዲሁም ደንብና መመሪያ ተጠብቆ ለአመልካቹ ምላሽ ይሰጥ›› በማለት ጽፏል፡፡ እነዚህን ለአብነት ያህል አቀረብን እንጂ ሌሎች ተቋማትም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ደብዳቤዎችን ለዞኑ ትምህርት መምሪያ ጽፈዋል፡፡

በአንድ መንግስት የሚመሩ እና ለአንድ አገር የሚሰሩ እነዚህ ተቋማት ግን አንዱ የአንዱን መመሪያ መቀበል ባለመቻላቸው መምህሩ ራሱን እና አገሩን ሳይጠቅም አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በወቅቱ ከስራ እንዴት ሊታገዱ እንደቻሉ ዝግጅት ክፍሉ ለማጣራት ተንቀሳቅሷል፡፡

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ መምህሩ ተቀጥረው ለዓመታት ይሰሩ የነበሩበት ትምህርት ቤት እያለ ያለፈቃዳቸው ለምን ወደ ሌላ ትምህርት ቤት እንደተዘዋወሩ፣ የመልቀቂያ ደብዳቤ ከማስቢራ ትምህርት ቤት መጻፍ እያለበት እንዴት ከዱባንቾ ትምህርት ቤት ሊጻፍ ቻለ ስንል ላቀረብንው ጥያቄ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጋሼ፤ ችግሩ ከተፈጠረ ከስምንት ዓመት በላይ መሆኑን በማስታወስ፤ በወቅቱ የነበሩ የስራ ኃላፊዎችን ጠይቀው እና ሰነዶችን አገላብጠው ስለተፈጠረው ነገር በሰጡት ምላሽ መምህሩ ከማስቢራ ትምህርት ቤት ለትምህርት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መሄዳቸውን አረጋግጠውልናል፡፡ 

መምህሩ ትምህርቱን ጨርሶ እስኪመለስ በማስቢራ ትምህርት ቤት የመምህራን እጥረት በማጋጠሙ በመምህሩ ቦታ ሌላ መምህር መቀጠሩን ነው የተናገሩት፡፡ መምህሩ ትምህርቱን ጨርሶ ሲመለስ ዱባንቾ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመድበዋል፡፡  መምህሩ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ሰርተው የመጡ እንደመሆናቸው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መመደብ ነበረባቸው ነው የሚሉት፡፡ ነገር ግን በወረዳው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ስለሌሉ በዱባንቾ እንዲመደቡ መደረጉንም ይገልጻሉ፡፡

መምህሩ ደግሞ ‹‹በሆሳዕና ከተማ ውስጥ በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መመደብ ካልሆነም ለትምህርት ከመሄዳቸው በፊት በነበሩበት ማስቢራ ትምህርት ቤት ስራዬን መቀጠል አለብኝ›› የሚል አቋም ይዘው እንደነበር ያነሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ዱባንቾ ትምህርት ቤት ለማስተማር ፈቃደኛ አልነበሩም ነው የሚሉት፡፡ ዱባንቾ ትምህርት ቤት ተደጋጋሚ ማስታውቂያዎችን አውጥቶ መምህሩ ማመልከት ባለመቻላቸው ከስራ ታግደዋል ብለዋል፡፡

አንድን መምህር ከሚያስተምርበት ትምህርት ቤት ያለፈቃዱ ማስነሳት እና በማይፈልግበት ትምህርት ቤት አስተምር መባሉ ከህግ አንጻር እንዴት ይታያል? ወረዳው የህግ ጥሰት አልፈጸመም ብለው ያስባሉ ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች አቅርበንላቸው ነበር፡፡ ቀደም ሲል ላቀረብንላቸው ጥያቄዎች በጥሩ ስሜት ምላሽ ይሰጡ የነበሩት አቶ ብርሃኑ፤ ‹‹እንዲያውም በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ በላይ መናገር አልችልም›› በማለት ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪ ሰርተው የተመለሱት መምህር ተደጋጋሚ ማመልከቻዎችን ሲያስገቡ እና ከዞን መምህራን ማህበር፣ ከክልል መምህራን ማህበር፣ ከክልሉ ትምህርት ጽህፈት ቤት፣ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ለተጻፉት ተደጋጋሚ ደብዳቤዎች ለምን ምላሽ መስጠት እንዳልተቻለ የዞኑን ትምህርት መምሪያ ጠይቀናል፡፡

በመምሪያው የመምህራን እና ሰራተኞች አስተዳደር አቶ ግርማ ዮሃንስ መምህር ገዛኸኝ ለዝግጅት ክፍሉ ያቀረቡት ቅሬታ ትክክል መሆኑን ይናገራሉ፡፡ መምህሩ ከዩኒቨርሲቲ ዲግሪያቸውን ይዘው የተመለሱበት ወቅት ዲግሪ ያላቸው መምህራን ዞኑ ይመድብ እንደነበርም ይመሰክራሉ፡፡

መምህራኖቹ ይሰሩበት በነበሩበት ወረዳ ውስጥ በሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲመደቡ ሲደረግ እንደነበርና መምህራን ይሰሩ በነበሩባቸው ወረዳዎች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከሌለ ደግሞ በሆሳዕና ከተማ ውስጥ እንዲሰሩ ሲደረግ መቆየቱን ይጠቅሳሉ፡፡ አቶ ገዛኸኝ ሲያስተምሩ የነበሩበት ሌሞ ወረዳ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አልነበረም፡፡ በመሆኑም ሆሳዕና ከተማ መግባት ነበረባቸው ነው የሚሉት፡፡

አቶ ግርማ እንደሚሉት ሆሳዕና ከተማ አቶ ገዛኸኝ በተማሩበት በታሪክ እና ስነዜጋ ክፍት ቦታ ስለሌለው እና ክፍት ቦታ እስኪገኝ የዞኑ ትምህርት መምሪያ አቶ ገዛኸኝን ሊሳና ቁሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ እንዲሰሩ መመደቡን እና አቶ ገዛኸኝ ወደተመደቡበት ሄደው ለማስተማር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የስራ ውላቸው መቋረጡን ያነሳሉ፡፡

ከዚያ በኋላም አቶ ገዛኸኝ ህመም ስላጋጠማቸው ዞን መጥተው ጉዳያቸውን በተከታታይ መጠየቅ አቁመው እንደነበር እና አልፎ አልፎ ግን መጥተው ጠይቀው ይመለሱ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በሆሳዕና ከተማ ውስጥ በግል ትምህርት ቤቶች ያስተምሩ ስለነበር በመንግስት ትምህርት ቤቶች ለማስተማር እምብዛም ፍላጎት አልነበራቸውም ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥም ከስራቸው ከተነሱ ሁለት ዓመት በላይ ስለሆነ ክፍት ቦታዎች ላይ መመደብ እንዳልተቻለ አንስተዋል፡፡

በዞኑ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስኪገኙ መምህሩ መጀመሪያ ይሰሩ የነበሩበት ትምህርት ቤት ውስጥ ሆነው እንዲቆዩ ለምን አልተደረገም በሚል ለአቶ ግርማ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በወቅቱ በቦታው ስላልነበርኩ አላውቅም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

መምህር ገዛኸኝ ግን በአቶ ግርማ ሀሳብ አይስማሙም በወቅቱ በሆሳዕና ከተማ ውስጥ ክፍት ቦታ አልነበረም የተባለው ሀሰት ነው ይላሉ፡፡ በርካታ ክፍት የስራ ቦታዎች ነበሩ፡፡ እንዲያውም በመደበኛ መርሃ ግብር በሀምሌ 2001 ዓ.ም ተመርቀው የተመለሱት አቶ ገዛኸኝ እያሉ በመስከረም 2002 ዓ.ም በክረምት ትምህርታቸውን ጨርሰው የመጡ በርካታ መምህራኖች በሆሳዕና በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ መመደባቸውን ይናገራሉ፡፡

‹‹እንዲያውም እኔ  በሰለጠንኩበት የትምህርት ዘርፍ አራት መምህራኖች ስለመመደባቸው መረጃ አለኝ፡፡ ይህንን ነገር የዞኑ መምህራን ማህበርም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ እኔ እንዳልቀጠር ሆን ተብሎ የተሰራ ስራ ነው›› ብለዋል፡፡

ምንም አይነት የጤና ችግር እንዳላጋ ጠማቸው የሚናገሩት አቶ ገዛኸኝ አቶ ግርማ ምክንያት አድርገው ያነሱት የጤና ችግር ጉዳይ ተገቢነት የሌለው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከ2001 ዓ.ም እስከ 2005 ዓ.ም ከወረዳ እስከ ፌዴራል ለተለያዩ አካላት ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ እንደነበር የሚያስረዱት መምህር ገዛኸኝ ጉዳዩን በየወቅቱ አይከታተልም የተባለውን እውነታነት የሌለው ነው ይላሉ፡፡ መምሪያው በሊሳና ቁሳ ትምህርት ቤት መድቦ እንደነበርም አላውቅም ያሉት መምህሩ በግል ትምህርት ቤት ማስተማር የጀመሩትም የመንግስት ስራ ለአንድ ዓመት ከግማሽ ጠብቀው ልጆቻቸው በርሃብ እንዳይሞቱ በማሰብ መሆኑን በመጠቆም፤ በመንግስት ትምህርት ቤት ለመስራት ፍላጎት ስለሌለኝ አይደለም፡፡ ‹‹ፍላጎት ባይኖረኝ ለምን ከወረዳ እስከ ፌዴራል አቤቱታ አቀርባለሁ›› ብለዋል፡፡

የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት መምህሩ ቀድሞ ያስተምሩ የነበሩበት ትምህርት ቤት ክፍት ቦታ ባለመኖሩ ዱባንቾ ትምህርት ቤት ተመድበው በስራ ገበታ ባለመገኘታቸው ከስራ መታገዳቸውን እንደምክንያት ሲያቀርብ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ደግሞ በዞኑ በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ክፍት ቦታ እስኪገኝ ሊሳና ቁሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመድበው በተመደቡበት የስራ ገበታ ላይ ባለመገኘታቸው ከስራ መታገዳቸውን በምክንያትነት አቅርቧል፡፡

በአንድ ዞን ውስጥ የሚገኙ ሁለቱም ተቋማት መምህሩን እንዴት አድርገው ሁለት ቦታ እንደመደቡ ለሚሰማው ሰው ግር የሚያሰኝ ነው፡፡ መምህሩ ደግሞ የትም ቦታ መመደባቸውን አላውቅም ማለታቸው ደግሞ ይባስ የሚገርም ነው፡፡ ከዞኑም ይሁን ከወረዳው ስለ መመደባቸው በእጃቸው የደረሰ መረጃም እንደሌላቸው ለዝግጅት ክፍሉ ገልጸዋል፡፡

የወረዳው ትምህርት ቤት በመምህሩ ቅሬታ ዙሪያ በቀጣይ ምን አቅጣጫ እንደያዘ የተጠየቁት አቶ ብርሃኑ ጋሼ ስራ ለቆ ተመልሶ ወደ ስራ መግባት ሂደቱ ከባድ ነው፡፡ ተወዳድሮ እንዲገባ ማድረግ ይቻላል፡፡ ማወዳደር እና ቅጥር መፈጸም ያለበት ዞኑ ሲሆን ዲግሪ የያዙ በመሆናቸው የስራ ልምዳቸውን ታሳቢ አድርጎ ቅጥር መፈጸም ያለበት ዞኑ ነው ብለዋል፡፡

በዞኑ ትምህርት መምሪያ መምህራን እና ሰራተኞች አስተዳደር አቶ ግርማ ዮሃንስ በቀጣይ  ከክልል ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር የመምህሩ የትምህርት ደረጃ እና የአገልግሎት ዘመን ታይቶ ምደባ ሊሰጣቸው ‹‹እንደሚችል›› ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ከስራቸው ተፈናቅለው የቆዩበትን ጊዜ ደመወዝ እንደማይከፈላቸው አብራርተዋል፡፡

አገሪቱ ካላት ውስን ሃብት በመቁረስ በተለያዩ መርሃ ግብሮች መምህራኖችን የምታሰለጥነው  የመምህራንን አቅም ለማጎልበት ነው፡፡ በትምህርትና ስልጠና ባጎለበቱት አቅማቸው ብቁ ዜጎችን እንዲያፈሩ፣ አገሪቱም የነገ አገር ተረካቢ እንድታገኝ በማሰብም ጭምር መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ መምህር ገዛኸኝ ግን በተለያዩ ውስብስብ ምክንያቶች በሰለጠኑት ሙያ ራሳቸውን እና አገራቸውን እንዳይጠቅሙ ተደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ላለባት አገር ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡

አሁንም ቢሆን የመምህሩን ቅሬታ መፈታት ይኖርበታል፡፡ መምህሩ ባካበቱት ልምድና ባሻሻሉት አቅም አገራቸውን እና ህዝባቸውን እንዲያገለግሉ መደረግ አለበት፡፡ ዞኑም ይህንኑ ከግንዛቤ በማስገባት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ አፋጣኝ ውሳኔ ሊወስን ይገባል እንላለን፡፡ 

መላኩ ኤሮሴ

Published in ፖለቲካ

በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የራስ ኃይል አስፋልት መንገድ ጥገና  ስራዎች  ዳይሬክተር

  የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ከአሁን ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መጠነ ሰፊና ሁሉን አቀፍ የመንገድ ጥገና አከናውኗል፡፡ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳየው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በእቅድ ከተያዘው የ84 ኪሎሜትር የአስፓልት መንገድ ጥገና 132 ኪሎሜትር ማከናወን የተቻለ ሲሆን ይህም አፈፃፀሙ በእቅድ ከተቀመጠው በላይ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ለመሆኑ በመንገድ ጥገና ዘርፍ ምን የተለየ ስራ ቢሰራ ነው ከእቅድ በላይ አፈፃፀም ማምጣት የተቻለው? ፣በጥገናው ረገድ የነበሩ ክፍተቶችስ ምን ነበሩ? በሚሉና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የራስ ኃይል አስፋልት መንገድ ጥገና ስራዎች  ዳይሬክተር ከሆኑት ከኢንጂነር መኮንን ጥበቡ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

 አዲስ ዘመን፡-  በ2009 የመጀመሪያው ግማሽ አመት በመንገድ ጥገና የነበረው አፈፃፀም በጣም ከፍተኛ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ለመሆኑ አፈፃፀሙ ከፍተኛ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው?

ኢንጂነር መኮንን፡- በበጀት አመቱ 84 ኪሎሜትር የአስፓልት መንገድ ለመጠገን አቅደን 132 ኪሎሜትር ማሳካት ችለናል፡፡ ይህም አፈፃፀማችን በጣም ከፍተኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ለጥገናው ዘርፍ ትልቅ ትኩረት መስጠታችን የስኬቱ አንዱ ሚስጥር ነው፡፡  ከዚህ በፊት ለመንገድ ጥገና ከሚያዘው በጀት በአንፃራዊነት በአሁኑ አመት የተሻለ መሆኑም ለመንገድ ጥገናው ከፍተኛ አፈፃፀም የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ በሰራተኛው ላይ ጥሩ የሆነ መነሳሳት እንዲኖር ተከታታይነት ያለው ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በየጊዜውም ሰራተኛው የሚያከናውናቸው ስራዎች ከጊዜ፣ ከጥራትና ደህንነት ከመጠበቅ አንፃር  ስለሚገመገም ይህም ለአፈፃፀሙ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

 አዲስ ዘመን፡- በሁለተኛው ግማሽ አመትስ የነበረው አፈፃፀም ምን ይመስል ነበር? ምንስ የተለየ ስራ ተሰርቷል?

 ኢ/ር መኮንን፡- የመጀመሪያውን ግማሽ አመት አፈፃፀማችንን መነሻ በማድረግና እቅዳችንን በመከለስ በበጀት አመት ውስጥ ከተያዘው 84 ኪሎሜትር የአስፋልት መንገድ ጥገና 65 ኪሎሜትር ማከናወን ተችሏል፡፡ ይህም ከመጀመሪያ ግማሽ አመት አፈፃፀም ጋር ሲወዳደር ተመሳሳይና አፈፃፀሙም ከመቶ ፐርሰንት በላይ ነው፡፡ በመጀመሪያው ግማሽ አመት የነበረንን ከፍተኛ አፈፃፀም ይዘን ስለቀጠልን በሁለተኛው ግማሽ አመትም ይህንኑ  መድገም ችለናል፡፡ ያልተቋረጡ ስልጠናዎችን ለሰራተኞቻችን መስጠት ችለናል፡፡ በጥገና ስራው ላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በስራ ላይ ለማዋል የጃፓን የልማት ተራድኦ ድርጅት ድጋፍም ጉልህ ነበር፡፡ በሌሊትም ጭምር ሳይቆራረጥ ስራዎችን መስራትና ለሰራተኞቻችን ክትትል አድርገናል፡፡ በተለይ ደግሞ ሰራተኞችን ለማነሳሳትና ለማነቃቃት የተለያዩ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የተሻለ አፈፃፀም ላመጡ ሰራተኞች ወይም ቡድን ማበረታቻ ማድረጋችን የበለጠ ውጤታማ እንድንሆን ረድቶናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በመንገድ ጥገና ዋነኛ ችግሮች ምን ነበሩ? የተወሰዱ የመፍትሄ ርምጃዎችስ?

ኢ/ር መኮንን፡- የመንገድ ጥገናው በዋናነት በሌሊት ከመከናወኑ አንፃር አልፎ አልፎ  ጠጥተው የሚያሽከረክሩ በመኖራቸው የባለስልጣን መስሪያቤቱ ማሽኖች ይገጫሉ፡፡ ይህም ከማሽኖቹ መገጨት ባሻገር በሰራተኞች ደህንነት ላይ የራሱ አሉታዊ  ተፅእኖ አሳድሮ ነበር፡፡ ከክፍለከተሞች ፖሊስ ጋር በመነጋገርና እገዛ በማግኘት ድጋፍና ክትትል አድርገውልናል፡፡ በጥገናው ረገድ ብዙ የሰራን ቢሆንም አሁንም ጥገና የሚያስፈልጋቸው መንገዶች በመኖራቸው ይህን ተደራሽ ለማድረግ  ለቀጣይ አመት እቅድ እየሰራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በሰራተኛው ላይ የአመለካከት ለውጥ በማምጣትና የለውጥ መሳሪያዎችን በመጠቀም በኩል ያለው አፈፃፀም ምን ይመስላል?

ኢ/ር መኮንን፡- መጀመሪያ ላይ ሰራተኛው ስራውን በአብዛኛው የሚያከናውነው ሌሊት ከመሆኑ አኳያ  ከደህንነት አንፃር የሚያነሳቸው በርካታ ችግሮች ነበሩ፡፡ እነዚህን ነገሮች ከሞላ ጎደል ለሰራተኞች ማሟላት ችለናል፡፡ ይህም በሰራተኛው ላይ ትልቅ መነሳሳት ፈጥሯል፡፡ በየጊዜው የማነቃቂያ ስልጠናዎችን እንሰጣለን፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙም ከሰራተኛው ጋር ቁጭ ብለን እንነጋገራለን፡፡ እያስተካከልን የምንሄድበት ሁኔታም አለ፡፡ ይህም በሰራተኛው ዘንድ ጥሩ  አመለካከት እንዲኖረው በር ከፍቷል፡፡ የበላይ አመራሩም እየመጣ ሰራተኛውን መጎብኘቱ ሰራተኛው እንዲበረታታ አድርጓል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል ጥገናን በጥራት ከማከናወን አንፃር በርካታ ቅሬታዎች ይነሱ ነበር፡፡ አሁን ላይ ጥገናውን በፍጥነት ከማከናወን አንፃርስ ጥራቱ ላይ ተፅእኖ አላሳደረም?

ኢ/ር መኮንን፡- በመንገድ ጥገና የጥራት ችግር እንዳይኖር ትክክለኛውን የጥገና ሂደት ለመከተል ሞክረናል፡፡ አንዳንድ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን፣ መብራቶችን ፣መቁረጫ መሳሪያዎችን  በመጠቀም የጥገና ስራውን ለማከናወን ሞክረናል፡፡ የጥገናውን ስራ የሚቆጣጠር በመንገድ ፈንድ ፅህፈት ቤት የተመደበ ስራውን የሚከታተል አደራ ኢንጂነሪንግ መድበናል፡፡ በተመሳሳይም ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የመንገድ ጥገና ስራውን የሚቆጣጠር ከላብራቶሪ፣ ጥራትና ቁጥጥር ክፍል የተውጣጣ የሞኒተሪንግ ቡድን እንዲመደብ አድርገናል፡፡ በዚህም መሰረት የጥራቱን ችግር ለመቅረፍ ጥረት አድርገናል፡፡ በመሆኑም በፊት ከነበረው አንፃር ብዙ ሄደናል፡፡ ነገር ግን አሁንም በጥራት ረገድ የሚቀሩ ነገሮች አሉ፡፡ የጥራት ችግር ካለ ሰራተኛውን በስልጠና፣እውቀቱን በማጎልበት ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት አድርገናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- መንገዶች ተጠግነው ወዲያውኑ ለትራፊክ ክፍት ሲሆኑ በመንገዶቹ ቆይታና ደህንነት ላይ ችግር አይፈጥርም?

ኢ/ር መኮንን፡- ስራው የመንገድ ጥገና ከመሆኑ አንፃርና ጥገናውም የሚከናወነው በከተማ ውስጥ በመሆኑ መንገዶቹን ጠግኖ ወዲያውኑ ለትራፊክ ክፍት ከማድረግ ውጪ አማራጭ የለንም፡፡ ነገር ግን ጥገናው  የሚፈለገውን የኮምፓክሽን ቆይታ፣ ጥራትና፣ የአስፋልት መጠን እስካሟላና ትክክለኛውን ደረጃ እስከጠበቀ ድረስ ምንም አይነት ችግር አይፈጥርም፡፡

አዲስ ዘመን፡- አሁንም ድረስ ጥገና ያልተዳረሰባቸው መንገዶችስ በባለስልጣኑ በኩል እንዴት እየታዩ ነው?

ኢ/ር መኮንን፡- ጥገና ያልተዳረሰባቸው መንገዶች በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚታወቁ ናቸው፡፡ ነገርግን አብዛኞቹ በአዲስ መልክ እንዲሰሩ ለኮንትራክተሮች የተላለፉ ናቸው፡፡ ለአብነትም ከላምበረት በኮተቤ ካራ የሚወስደው መንገድ ይጠቀሳል፡፡ የጥገናውን ስራ ስንሰራ ቅድሚያ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን በመለየትና በፌዝ በመከፋፈል ነው፡፡ በሚቀጥለው በጀት አመትም በጥገና ያልደረስንባቸው አካባቢዎች ላይ እንገባለን፡፡ በክረምቱ ወቅትም ችግር ፈቺ ጥገናዎች ባናደርግም ጊዜያዊ ጥገናዎችን  አከናውነናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአጠቃላይ በበጀት አመቱ በመንገድ ጥገና ረገድ የነበረው አፈፃፀም ምን ይመስላል?

ኢ/ር መኮንን፡- የጥገና ስራ ሲባል መንገድን ብቻ ሳይሆን የፍሳሽ ውሃ ማስወገጃ ቱቦዎችን፣ የእግረኛ መንገዶችንና የመንገድ ዳር መብራቶችን የሚያካትትና ሁሉን አቀፍ በመሆኑ እነዚህን ስራዎችን ሁሉ ለመስራት ሞክረናል፡፡  የጥገና ስራችን አስፋልትን ከመጠገን በዘለለ ሌሎች ጥገናዎችንም የሚያካትት ነው፡፡ አደባባዮችን በማፍረስ በመብራት እንዲለወጡም አድርገናል፡፡ ይህም ከመንገድ ጥገና ውጪ የሰራነው ተጨማሪ ስራ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ጨምረው በአጠቃላይ የጥገናው ስራ ከሚፈለገው በላይ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ባጠቃላይ አፈፃፀማችን ፣የሰራተኛው አመለካከትና ከውጪ የሚመጣው ግብረመልስ ጥሩ የሚባል ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የቀጣይ እቅዳችሁ ምንድን ነው?

ኢ/ር መኮንን፡- ቀደም ሲል የጥገና ስራው በሶስት ቡድን ብቻ ይሰራ ነበር፡፡ ነገር ግን  በቀጣዩ አመት የጥገና ክፍሉን ወደ አምስት ቡድን ከፍ ማድረግ  ነው የፈለግነው፡፡ ይህም ሲሆን በመንገድ ጥገና ረገድ ያለው ተደራሽነት ይሰፋል፡፡ ይህም የሰው ኃይል በማሟላትና የጥገና መሳሪያዎችን በመጨመር የሚከናወን ይሆናል፡፡ ከዚህም ባሻገር አምስት ሪጅኖችን አዋቅረናል፡፡ ከሪጅኖቹ በሚመጣው ዳታ መሰረት እኛ ጥገናውን ለመስራት ተዘጋጅተናል፡፡ አስፈላጊ የሚባሉ መሳሪያዎችን በመጠቀምና ተጨማሪ የሰው ኃይልና ባለሙያዎችን በመጨመርና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም  ከዘንድሮው በተሻለ በተደራሽነትም በጥራትም ለመስራት አቅደናል፡፡ አሁን የዝግጅት ስራ ላይ ነው ያለነው፡፡ የ2010 እቅድ እያወጣን ነው፡፡ ቅድሚያ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን መንገዶች በመለየት ለመስራት እያቀድን ነው፡፡ 

  አስናቀ ፀጋዬ

Published in ኢኮኖሚ

ሥልጣናቸውን የለቀቁት የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሸሪፍ

 

የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሸሪፍ የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከኃላፊነታቸው ካገዳቸው በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል። ቀጣይስ ምን ይፈጠራል? ለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምን ስልጣናቸውን ለቀቁ? የእርሳቸውን ስልጣን መልቀቅ ተከትሎስ በቀጣይ ምን ይሆናል? የሚለውም የሰሞኑ የመገናኛ ብዙሃን ዋነኛ አጀንዳና መነጋገሪያ ሆኗል።

እንደ መገናኛ ብዙሃኑ ዘገባም፤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን መውረድ «ፓናማ ፔፐርስ፤ የፓናማ ሰነዶች» በሚል የሚታወቁት የሚስጥር ሰነዶች ቀዳሚና ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው። እነዚህ ሰነዶች በርካታ የቀድሞና የወቅቱ መሪዎች፤ የቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከፍተኛ ባለስልጣኖች፣ ባለሀብቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች በተለያዩ መንገዶች ያገኙትን ከፍተኛ ገንዘብ በአገራቸው በሚገኙ ባንኮችና ሌሎች ተቋሞች በማስቀመጥ በህጋዊ መንገድ ተጠቃሚ ከመሆን ይልቅ በድብቅ ወደውጭ እያሸሹ በምስጢር ኩባንያዎችና አክሲዮኖች ስም ከግብር ነፃ በሆነ መንገድ በማትረፍ ህገወጥ ተግባር ላይ በስፋት መሰማራታቸውን ያረጋግጣሉ።

በዚህ መንገድ ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦች ስምና ሌሎች መረጃዎች የያዙት እነዚህ ሰነዶች ከ11ሚሊዮን በላይ ሲሆኑ፤ «ሞሳክ ፎንሴካ» በተባለና ከአርባ ዓመታት በላይ ሲሰራ የቆየው የፓናማ የጥብቅና ድርጅት ስር የነበሩ ናቸው።

ድርጅቱ የአፍሪካን የሚገኙትን ጨምሮ የበርካታ አገራት መሪዎች፤ ከፍተኛ ባለስልጣኖች፣ ባለሀብቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ከአገራቸው የሚያሸሹትን ገንዘብ ኩባንያዎችን ያቋቋሙ አሊያም አክሲዮኖችን የገዙ በማስመሰል ከግብር ነፃ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን የማመቻቸትና ህገ ወጥ ገንዘብ ሕጋዊ እያስመሰለ የማዘዋወር ብቃት ያለው ነው። ከውጭ አገሮች በሕገወጥ መንገድ የሚወጣውን ገንዘብ የሚያስቀምጠው ወይም በሥራ ላይ እንዲውል የሚያደርገውም በተለያዩ አገራት በሚያቋቁሟቸው የምስጢር ኩባንያዎች ነው።

ድርጅቱ በምስጢር ጠባቂነታቸው ከታወቁ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት መካከል አንዱ ምናልባትም ግንባር ቀደሙ እንደሆኑም መሪዎችን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ገንዘባቸው እንዲጠበቅ አሊያም በስራ ላይ እንዲያውል ግንባር ቀደም ኃላፊነቱን ይሰጡታል።

ይሁንና ከሁለት ዓመት በፊት የድርጅቱ የምስጢር ሰነዶቹ ማንነቱ ባልተገለፀ የመረጃ ምንጭ አማካኝነት ይፋ ወጥተዋል። የምስጢር ጠቋሚ ግለሰብም ሰነዶቹን «ሱዴች ዛይቱንግ» ለተባለው የጀርመን ጋዜጣ ያቀበለ ሲሆን፤ ጋዜጣውም ከዓለም ዓቀፉ የምርመራ ጋዜጠኝነት ኅብረት ጋር በመተባባር ከሰማንያ አገራት መገናኛ ብዙኃን በተውጣጡ ጋዜጠኞች አማካኝነት ምርመራ ካደረገ በኋላ ሰነዶቹን ይፋ አድርጓቸዋል።

ከዚህ ምስጢራዊ ሰነድ ጋርም በሕገወጥ መንገድ ገንዘብ በማሸሽና ከግብር ነፃ በሆነ መንገድ አትራፊ ለመሆን የሚታትሩ  በርካታ የዓለማችን መሪዎች ስም አብሮ ወጥቷል። የቀድሞው የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን፣ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን፣ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ፣ የሶሪያ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ፣ የሊቢያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ፣ እንዲሁም የግብፅ የቀድሞ መሪ ሆስኒ ሙባረክ ይገኙበታል።

የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሸሪፍም የዓለም ባለፀጐችና ባለሥልጣናት ገንዘብና ንብረታቸውን እንዴት ከሕዝብ ሸሽገው ከግብር አርቀው እንደሚያስቀምጡ ከሚያስረዳው ሰነዱ ጋር የሚተሳሰር ስም ካላቸው መሪዎች አንዱ ናቸው። የሚስጠራዊን አደባባይ መውጣት ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሰነዱ በልጆቻቸውና በሃብታቸው ዙሪያ ያወጣውን ዘገባ ሲያስተባብሉና የቤተሰባቸው ሃብት በህጋዊ መንገድ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው አስቀድሞ ያካበቱት እንደሆነ ለማሳመን ሲወተውቱ ቆይተዋል። የጉዳዩ እያደር ትኩስ መሆን ትኩሳት የሆነበት የፓኪስታን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ታዲያ ጉዳዩ እንዲመረመር ትዕዛዝ አስተላልፏል። በትዕዛዙ መሰረተም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላለፉት አስራ አምስት ወራት የተለያየ ምርመራ ሲካሄድባቸው ቆይቷል።

የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሙስና ጋር በተያያዘ የቤተሰባቸውን ሀብት ካጣራ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ልጆቻቸው ከሀገር ውጭ ኩባንያ እንዳላቸው አረጋግጧል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከገቢያቸው በላይ ኑሮን እየኖሯት መሆኑንና በዱባይና በለንደን በርካታ ሃብትና ንብረት እንዳላቸው በማረጋገጥ ከስልጣናቸው እንዲታገዱም በሙሉ ድምጽ ወስኗል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የሙስና ዶሴ እንዲከፈትና ክስ እንዲመሰረትባቸው የተጠየቀ ሲሆን፤ ክሱ ደግሞ ልጆቻቸውን፤ የሀገሪቱን የገንዘብ ሚኒስተር ኢሻቅ ዳርና ሌሎችንም ይጨምራል ነው የተባለው።

ፓኪስታን ከቅኝ ግዛት ከተላቀቀችበት ከዛሬ ሰባ ዓመት በፊት አንስቶ ላለፉት ዓመታት አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትር ያገለገሉ መሪዎች አምስቱን ዓመት የስልጣን ዘመን ቆይታቸውን በሰላም አጠናቀው አያውቁም። አብዛኞቹ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ተገርስሰዋል፤ አሊያም በከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ከኃላፊነት ተነስተዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ በፓርቲያቸው ግፊት ቀሪዎቹ ደግሞ በግድያ ከስልጣን ተወግደዋል።

ናዋዝ ሸሪፍም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መንበረ ስልጣን ብቅ ያሉት በ1990 ነው። ይሁንና ስልጣናቸውን ማቆየት የቻሉት ለሶስት ዓመታት ብቻ ነበር። በ1997 ዳግም ወደ ስልጣን ቢመጡም ከሁለት ዓመት በኋላ በፔርዜዝ ሙሻረፍ መፈንቅለ መንግስት ስልጣናቸውን ተቀምተዋል። ለዓመታት ለስልጣን ርቀው ለሶስተኛ ጊዜ እኤአ በ2013 ወደኃላፊነት የመጡት ሸሪፍ፤ ላለፉት አራት ዓመታት አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል።

 በዚህ ሂደት አምስቱን ዓመት የስልጣን ዘመን ቆይታቸውን በሰላም በማጠናቀቅ የቀደመ ታሪክ ለመቀየርና አንድ ዓመት ብቻ የቀራቸው ሸሪፍም፤ ከሰሞኑ እንደወትሮው በኃይል ሳይሆን በሙስና ምክንያት በመጨረሻዋ ሰዓት ከስልጣን ወርደዋል።

እንደ መገናኛ ብዙሃኑ ዘገባም፤ ከሚስጥራዊ ሰነዶቹ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ቤተሰቦቻቸውና ጠበቃቸው ነፃ የሚያደርጋቸውን በቂ መረጃ ለአገሬው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረብ ሳይሆንላቸው ቀርቷል። ያቀረቧቸው መረጃዎች እውነት አልባና አሳማኝነት ጎድሏቸዋል። የሚሊየን ዶላር ክምችትም አንድ ዳኛ መግዛትና ውሳኔውን የማስለወጥ አቅም እንደሌለው ማረጋገጫ ሰጥቷል። በዚህ ሰነድ ቀውስ ስልጣናቸው በገዛ ፈቃዳቸው ሲለቁ ሸሪፍ የመጀመሪያው መሪ ግን አይደሉም። ከዓመት በፊት የአይስላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲግማንዱር ጉንላውግሰን ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል።

እንደ ዱራን ታይምስ የዜና አውታር የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ አዳም ጌሪ ከሆነ ግን ከሚስጥራዊ ሰነዱ የሙስናው ቅሌት ጀርባ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን መውረድ ምናልባትም የምዕራባውያንና ሌሎች አገራት እጅ አለበት። እንደፀሃፊው እምነት፤ ሰውየው የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሚና ደካማ ቢሆንም፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ረገድ አገራቸውን ተጠቃሚ የሚያደርግ ተግባራት በመከወን ረገድ ውጤታማ እንደነበሩ ይገልፃል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፓኪስታን በመወከል ባህር ስንጠቃ ጉዞዋን ለምታቀላጥፈው መርከብ ዋነኛው ካፒቴን ናቸው። በተለይ በዲፕሎማሲው መሰክ ሰውየው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከቻይና ከኢራን ጋር ከኢኮኖሚም ሆነ በወታደራዊ አጋርነት የመሰረቱት ጥሩ ወዳጅነት በተለይ «በአንድ መቀነቱ» የቻይና የንግድ ፖሊሲ ይሁንታ መቸራቸውና የቻይና ፓኪስታን የኢኮኖሚ ኮሪደር ተግባራዊ እንዲሆን በመፈቀዳቸው ቅናትና ስጋት ያደረባቸው አገራት አሉ። ፍላጎታቸውም ሁለቱንም አገራት የማዳከም ነው።

ምንም እንኳን የአገሪቱ የውስጥና የውጭ ፖለቲካል መዘውር በአንድ ሰው እጅና እጣ ፈንታ ላይ እንደሆነ ባይታመንም የሰውየው ቁልፍነት ግን አይካድም። ይህ እስከሆነም፤ ለሰውየው ከስልጣን መውረድ የአንዳንድ አገራት የምዕራባውያን እጅ እንዳለበት እሙን ነው። ጎረቤቷሞቹ ህንድና ፓኪስታን በካሽሚር ግዛት ሁሌም ቢሆን ስምምነት ኖራቸው አያውቅም። እናም የኒውዴሊ መንግስት ለሰውየው መውረድ አስተዋፆኦ አበርከቷል ተብሎ በመገናኛ ብዙሃኑ ከተገመቱ አገራት መካካል አንደኛው ሆኗል። ህንድ በአንፃሩ  በጉዳዩ ላይ እስካሁን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች። የቢቢሲው ዘገባ፤ ኢያስ ካሃን፤ ከሆነ ደግም ምክንያቱ፤ ለዘመናት የዘለቀ የአገሪቱ የፖለቲካ ኡደትና የህዝብን ድምጽ የመወሰን መብት የመገደብ አካሄድ መሆኑን አትቷል።

የሰውየው ከስልጣን መውረድ መሰል ምክንያቶች መደርደር ቢቻልም፤ የሚስጥራዊ ሰነዱ ቅሌት ግን በቀጣዩ ዓመት አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በዋዜማ ላይ ለምትገኘው ፓኪስታን ትልቅ ዱብ እዳ ነው። እንደ ኤኤፍ ፒ ዘገባ፤ አገሪቱ አሁን ላይ መንግስት አልባ ናት። እናም ከአገራዊው ምርጫው በፊት ሰውየውን በቶሎ መተካት ይቀድማል።ምንም እንኳን የሰውየው ምትክ በቀናት ውስጥ የሚካሄድ ቢሆንም፤ ከቀጣዩ ዓመት በፊት አገራዊ ምርጫ ማካሄዱ ግን አይታሰብም። ይልቅስ ሰውየውን ማን ሊተካው ይችላል የሚለው አሳሳቢ ነው።

ምንም እንኳን ሰውየው ከስልጣን ቢወርዱም የአገሪቱ ዋነኛ ፓርቲ የበላይ ተጠሪ ናቸው። ፓርቲያቸውም 342 መቀመጫ ካለው የአገሬው ፓርላማ 209 የሚሆነው መቀመጫ በበላይነት የተቆጣጠረ ነው። ይህ እንደመሆኑም የሰውየው ምትክ ሌላ የፓርቲው አባል እንደማይሆን እርግጥ ነው። ለሰውየው ምትክነት ወንድማቸው ሰሃባዝ ከፍተኛውን ቦታ ቢወስዱም፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቢሆን ተወዳዳሪያቸውን በማቅረብ የእድላቸውን መሞከራቸው ግን አይቀሬ ነው።

እንደ አልጀዚራ ዘገባ፤ የአገሪቱ ፓርላማ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምትከ ለመምረጥ ዛሬ ይሰበሰባል። እንደ ቪኦኤ ዘገባ ከሆነ ደግሞ ምንም እንኳን ምርጫው ይካሄድ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጋረጃው ጀርባ ሆነው አገራቸውን መምራታቸውን ይቀጥላሉ።

ላለፉት ሃያ ዓመታት በፖለቲካ ህይወት ውስጥ ያሳለፈውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህገ ወጥ ገንዝብ ማከማቸታቸውንና በሙስና መዘፈቃቸውን በተደጋጋሚ ሲገልፅ የሚሰማው የአገሬው ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ኢምራን ከሃን በአንፃሩ በቀጣዩ የአገሬው ምርጫ ብርቱ ፉክክር በማድረግና በማሸነፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተክቶ አገሪቱን በበላይነት እንደሚመራ ለሮይተርስ  ሲገልፅ ተሰምቷል። ባሳለፍነው ቅዳሜም በሺዎች የሚቆጠሩ የአገሬው ዜጎች በአገሪቱ ዋና ከተማ ኢስላማባድ ለኢምራን ከሃን ድጋፋቸውን ሲሰጡ ታይተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሻሪፍ ፓርቲ በሌላ ጎን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣን ኃላፊነታቸው ያከናወናቸው ውጤታማ ተግባራት በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው ምርጫው አሸናፊ እንዲሆን እንደሚያግዘው ተማምኗል። የፓርቲው ተጠሪ የሆኑት ከሃዋጅ ሳድራፊክ፤ፓርቲያቸው በአገሪቱ የበላይ ተቋም የተላለፈውን ውሳኔ በፀጋ እንደሚያከብር፣ እንደሚቀበልና አባላትና ደጋፊዎቻቸውም ከአምፅ ይልቅ በተረጋጋ መልኩ ጉዳዩን እንደሚከታተሉት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

አንዳንዶች በአንፃሩ በአገሪቱ ውጥረት እንደሚከሰት እርግጠኛ ሆነዋል።ታዋቂው የአገሬው ዋን ቲቪ ጋዜጠኛ ራሂም ሻምሲ የዚህ  እሳቤ ተጋሪ ነው። እንደ ጋዜጠኛው እምነት በቀጣዩ ዓመት አገራዊ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና ውጥረት መኖሩ አይቀሬ ነው።

ታምራት ተስፋዬ

Published in ዓለም አቀፍ

በየትኛውም አገር ውስጥ የሚገኝ መንግስት ለህዝቡ የተሟላ አገልግሎት መስጠት  እንዲችል ግብር መሰብሰቡ የግድ ነው። ከልማት የገቢ ምንጮች ውስጥ ዋነኛው በአገር ውስጥ የሚሰበሰብ ግብር መሆኑ እርግጥ ነው።

ግብር ከሌለ መንግስት ተግባሩን በሚፈለገው ሁኔታ ሊወጣ ካለመቻሉም በላይ አስፈጊነቱም ጥያቄ ውስጥ ይገባል። በሌላ በኩልም ህዝቡ መሰረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን አያገኝም። መሰረታዊ አገልግሎቶችን የማያገኝ ህዝብ ደግሞ እርካታ አይኖረውም።

አንዳንድ ወገኖች ኢትዮጵያ ውስጥ ግብር መክፈልን እንደ እዳ ይመለከቱታል። ይህ አስተሳሰብ እጅግ የተሳሳተ ነው። አስተሳሰቡን ለማረቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ያስፈልጋል። ግብር መክፈል ህጋዊ ብቻ አይደለም። የዜጎች ኩራትም ጭምር ነው።

ግብር ከፋይ ዜጋ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመረጠውን መንግስት አገልግሎት አሰጣጡን በተገቢው መንገድ ሊጠይቅ ይችላል። “እኔ እኮ ግብር ከፋይ ነኝ” ብሎ ማናቸውንም ግልጋሎት የማግኘት መብቱንም ይጎናፀፋል።

ሆኖም እንደ እኛ ባለ አገር ውስጥ ግብር መክፈል የአገርን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት፣ ኢኮኖሚው ጠንካራ እንዲሆንና ለህዝብ የሚሰራ መንግስት እንዲኖር ያደርጋል። እናም ኢትዮጵያ ውስጥ ግብር መክፈል የዜግነት ክብር ማረጋገጫ እንጂ ግዴታ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለዜጎቿ ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠርና የተጋረጠባትን የድህነት ፈተና ለመሻገር ብርቱ ጥረት እያደረገች ትገኛለች። ይህን ጥረቷን እውን ለማድረግም በቂ በጀት ያስፈልጋታል። ይህ በጀት ደግሞ ከየትም የሚመጣ አይደለም። ህዝቡ ለመንግስት ከሚከፍለው ግብር መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው።

ሀገራችን ውስጥ ያለው መንግስት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ እንደመሆኑ መጠን፤ የግሉ ባለሃብት ሊፈፅማቸው የማይችላቸውን ጉዳዮች መንግስት በተመረጠ አኳኋን ጣልቃ ገብቶ ይፈፅማል። ታዲያ ይህን ተግባር ለመከወን መንግስት ገንዘብ ያስፈልገዋል። የግሉ ባለሃብት በማይሰማራባቸው፣ ነገር ግን አብዛኛውን ህዝብ ተጠቃሚ ሊያደርጉ በሚችሉ የገጠር ልማቶችን ለመተግበር መንግስት በጀት ሊኖረው ይገባል።ይህን ተግባር ለመፈፀም ግብር ለማስከፈል የሚደረገውን ጥረት ግን በተለይ የተወሰኑት የንግድ ማህበረሰብ አባላት በአሉታዊ የማየት ዝንባሌ ሰሞኑን ታይቷል።

ከግብር ሁኔታ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎች አስገራሚ ተግባሮችን ሲያከናውኑ ተስተውሏል። ግብር መክፈል የዜግነት ክብር ቢሆንም፤ አንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎች ልማታዊ ነጋዴውን ጭምር በማሳሳት ግብርን በመቃወም ስም ዕቃዎችን ያለ አግባብ በመጋዘኖች በማከማቸት አሊያም ህዝባዊ አገልግሎትን በማቋረጥ ሆን ብለው የገበያ እጥረትን ለመፍጠር ያደረጉት ተግባር ፈፅሞ የተሳሳተ ነው።

እነዚህ ነጋዴዎች በዚህ ተግባራቸው በአንድ በኩል ዋጋ በማስወደድ የራሳቸውን ህገ ወጥ ትርፍ ለማግኘት የሞከሩ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የፀረ ሰላም ኃይሎች መጠቀሚያ ሆነው አገራችን ውስጥ  አመፅ እንዲነሳሳ ለማድረግ ጥረዋል። ታዲያ ይህን በግብር ስም የሚካሄድ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር መድፈቅ ይገባል። እንዲህ ዓይነቱ አሰራር አንዱን ጥሎ በሌላው ማጣት ላይ የሚደረግ የዜሮ ድምር ጨዋታ ስለሆነ መቆም ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ አገራችን አሁን በምትገኝበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ልዩነትን በሠላማዊ መንገድ መፍታት፣ መቻቻልን መሰረት ማድረግ እንዲሁም አንዱ ሲያገኝ ሌላው በልማታዊ ውጤቱ መጠን የሚያገኝበት ሁኔታ በመኖሩ ነው፡፡

ዳሩ ግን በዜሮ ድምር ውጤት አሰላለፍ፤ አንዱ ሲያገኝ የሌላው የማግኘት መብት በዚያው መጠን ይዘጋል፡፡ እናም በዚህ የጥሎ ማለፍ ውድድር ውስጥ መቻቻል የሚባል ነገር ከቶውንም ሊታሰብ አይችልም፡፡

ታዲያ ውድድሩ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ውስጥ የተንሰራፋ ከሆነ፤ ፖለቲካው ራሱ የዜሮ ድምር ጨዋታና ፀረ- ዴሞክራሲያዊ ከመሆን የዘለለ ዕጣ ፈንታ ሊኖረው የሚችል አይመስለኝም፡፡ በመሆኑም በዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ የዜሮ ድምር ውጤት የጥሎ ማለፍ የንግድ ውድድር እንዲዘጋ፣ በአስተሳሰቡ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች እጆቻቸው ሊሰበሰብ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ አሊያ ግን በሰበብ አስባቡ አንድ የሚያነጋግር ጉዳይ በተፈጠረ ቁጥር በኪራይ ሰብሳቢነት አባዜ መታመሱ በማንኛውም መስፈርት ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነትን አስተሳሰብና ተግባር የህዝቡን ሃብት ከመዝረፍ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው፡፡ እርግጥም የዘረፋ ድርጊትን ከኪራይ ሰብሳቢነት ለይቶ መመልከት አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አንድ ግለሰብ ሊኖረው የሚችለው የመዝረፍ ዕድል ሌላውም እኩል በሆነ ሁኔታ ሊያገኘው ስለማይችል ነው፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ ሁሉም እኩል ይዝረፍ እያልኩ አለመሆኑ ሊታወቅልኝ ይገባል። ከላይ እንዳልኩት የኪራይ ሰብሳቢነት አሰራር የዜሮ ድምር ጨዋታ ነው። በዚህ ጨዋታ  በዝርፍያው ውስጥ አንዱ ሲያገኝ የሌለው የማግኘት መብት በዚያው መጠን እንደሚዘጋ በግልፅ የሚያመላክት ነው፡፡

ለምሳሌ ያህል አንድ ባለሃብት ከመንግስት ኃላፊ ጋር ተመሳጥሮ በእከክልኝ ልከክልህ የጥገኝነት ቀመር የ10 ሚሊዮን ብር ዕቃ ከቀረጥ ነፃ በሆነ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ሲያስገባ፤ በዚያኑ ያህል ይህን ዕቃ በህጋዊ መንገድ አስገብተው ግብር እየከፈሉ የሚነግዱ በርካታ ዜጎችን ከገበያው ውድድር ውጪ ማድረጉ አይቀርም፡፡

ታዲያ በእንዲህ ዓይነቱ በአቋራጭ የመበለፀግ ፍላጎት ተጠቃሚዎቹ ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ናቸው፡፡ እናም አብዛኛው ህዝብ የበይ ተመልካች ሆኖ በልማት ውጤቱ መጠን ሃብት የሚያፈራበት ሁኔታ እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ ሰሞኑን በአንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎች የተካሄደው ተግባር ማሳያ ነው፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር ፀረ-ዴሞክራሲ በመሆኑም በመስማማት ላይ ተመርኩዞ ሊሰራ አይችልም፡፡ ከዚህ ይልቅ የመጠቃቀም ሰንሰለቶችን ከላይ እስከታች በመዘርጋትና ደጋፊን በማብዛት ዝርፊያን የማጧጧፍ አማራጭን ይከተላል፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር በሰፈነበት ሀገር ውስጥ ዴሞክራሲን መዝራት፣ በምድረ በዳ ላይ እህል በትኖ ሰብል ለማጨድ የማለም ያህል ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ሀገር ዴሞክራሲን ለማጎልበት ከፈለገ በቅድሚያ የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካከትና ተግባር ማምከን ይኖርበታል፡፡

መንግሥት እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም ይሁን ነገ የሚያካሂዳቸው ማናቸውም የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ተግባራት የዚህ መሰረታዊ እውነታ ውጤቶች መሆኑን ለመገንዘብ የሚያስቸግር አይመስለኝም። 

ሁላችንም እንደምንረዳው፤ በማንኛውም የመንግሥት የስራ ኃላፊነት ያሉ ግለሰቦች ህዝብን እንጂ ራሳቸውን ለመጥቀም አይደለም ወንበር ላይ የሚቀመጡት፡፡ እርግጥ ህዝብን ለማገልገል ቆርጠው የተነሱና ዴክራሲያዊ አስተሳሰብ ያላቸው ባለስልጣናት መኖራቸው አይታበይም፡፡

ምናልባትም እነዚህ ባለስልጣናት በሰሞኑ የኪራይ ሰብሳቢዎች ተግባራት ውስጥ አይሳተፉም ብሎ መደምደም አይቻልም። ያም ሆኖ አሁንም የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነቱን እንዳይዝ መንግስት ብርቱ ቁጥጥር ማድረግ አለበት። ህጋዊ እርምጃዎችንም መውሰድ ይገባዋል።

በተለይም መንግሥት የሁለተኛውን የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለማሳካት ሰፋፊ ስራዎችን ጀምሮ እያካሄደና በህዝቡ ከፍተኛ የለውጥ ስሜት ውጤት እያገኘ ባለበት በአሁኑ ወቅት የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር እንደ አላስፈላጊ ችካል ደንቃራ ሆኖ አላላውስ ማለት አይኖርበትም፡፡ በመሆኑም በጥገኝነት ላይ የጀመረውን የማጥራት ዘመቻ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

በመሆኑም በሙስና በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የተወሰደው አግባብነት ያለው እርምጃም “የጨለማው ዓለም ደራሲያን” እንደሚያስወሩት የፈጠራ ልቦለድ ሳይሆን፤ ህዝቡ በእጅጉ የተደሰተበት ተግባር ነው፡፡

በቀጣይነትም መዋቅሮቹን በጥልቀት በማጥናትና በመፈተሽ፤ የህዝቡን ተጠቃሚነት በይበልጥ ከሚያረጋግጠው የልማት ዕቅድ መንገድ ላይ ጥገኞችን ጥግ በማስያዝ ገለል ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ግብር መክፈል የአገር ኩራት ሆኖ ሳለ፤ በግብር መክፈል ሰበብ ዕቃ መደበቅና ማከማቸት እንዲሁም የዋጋ ንረት ለመፍጠር መሞከር ዋነኛው የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር በመሆኑ ሊወገዝ ይገባል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግስትም የማያወላውል እርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡

ዳዊት ምትኩ

Published in አጀንዳ

ሰሞኑን የቀን ገቢ ግምትን በአመቱ አባዝቶ የግብር መጠኑ አድርጎ የተገነዘበ ነጋዴ በብዛት እንዳለ ታይቷል፡፡ ይህ አይነቱ ችግር ሊፈጠር የቻለው፤ በቀን ገቢ ግምት አሰራሩ ዙሪያ ግልጽነት ባለመፈጠሩ ነው፡፡ ግልጽ ያልሆኑ ነገር ግን በቀላሉ ሊያግባቡ የሚችሉትን ነገሮች ለይቶ ሰፊ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ቢሰራ ኖሮ አንዳንድ ነጋዴዎች ከሱቆቻቸው እቃዎችን የመቀነስና በአንዳንድ ነጋዴዎች ደግሞ ተከስቶ የታዘብነው በቀን የሚያስገቡትን የገቢ መጠን የመደበቅ ዝንባሌ ጭምር ባልገጠመ ነበር፡፡

ነጋዴው በትክክል የሚከፍለውን የግብር መጠን ባለማወቁ ሁኔታዎቹ ሰፊ ቅሬታን ፈጥረው በአንዳንድ አካባቢዎች በተወሰነ ደረጃ ሱቆች እንዲዘጉ ምክንያት ፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሱቆች ለመዘጋታቸው አንዳንድ ነጋዴዎች ‹‹የተጣለብን ግብር ተጋንኗል›› የሚል በምክንያትነት ሲያቀርቡ፤ ቀሪዎቹ ሱቅ የዘጉት ደግሞ ሱቅ በመዝጋት ተቃውሟቸውን የገለጹ ነጋዴዎች የሚያደርሱባቸውን ጫና በመፍራት መሆኑን ሲገልጹ ተደምጧል፡፡

አሰራሩ ፍትሃዊ እንዲሆን ግምት የሚሰሩ ባለሙያዎች ከተለያየ ተቋም እንዲወከሉበት ተደርጓል፡፡ ከንግድ፣ ከፋይናንስና ከገቢ መዋቅር የተውጣጡ ባለሙያዎች በግምት አሰራሩ የተሳተፉ ሲሆን፤ ጥራቱን ለመጠበቅም የቁጥጥር ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡ የቁጥጥር ኮሚቴው በተለይ ከስነ ምግባር ጋር ተያይዞ ጥያቄዎችና ግምታዊ አሰራሩ ላይ በጣም የተጋነነ በአንጻሩም በጣም ያነሰ ግምት ከቀረበ እየፈተሸ ተገቢው ማስተካከያ እንዲሰጥበት  ያደርጋል፡፡

በዚህ ሂደት በርካታ ቅሬታ አቅራቢዎች ቅር ያላቸውን ጉዳይ አቅርበው ምላሽ አግኝተዋል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ‹‹የኔ ጉዳይ ምላሽ አያገኝም›› የሚል ድምዳሜ ይዘው ቅሬታ እያላቸው ህጋዊ ሂደቱን ተከትለው ያላቀረቡ ታይተዋል፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡ በርግጥ የቀረበ ቅሬታ ሁሉ ይስተካከላል ማለት አይደለም፡፡ ከንግድ እንቅስቃሴው ጋር በጣም የተጋነነ፣ ነባራዊ እንቅስቃሴውን የማይገልጽ ከሆነ ተፈትሾ የሚሻሻል ይሆናል፡፡ ከንግድ እንቅስቃሴው ጋር ተመጣጣኝ ግምት ከቀረበ ግን ግምቱ ይጸናል፡፡ ቅሬታ ስለቀረበ ብቻ ይሻሻላል ማለትም አይደለም፡፡ 

አንዳንዶች ይህንን ሂደት ባለመረዳት ለጥያቄያቸው ምላሽ ሊያስገኝ የማይችል ሂደት ሲከተሉ ተስተውሏል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ከኋላ ሆነው ቅስቀሳ የሚያደርጉና ‹‹ግብር እንዲቀነስ ሱቆቻችሁን ዝጉ›› በማለት የተሳሳተ መረጃ የሚሰጡ አካላት ባሳደሩባቸው ጫና መሆኑን ባለስልጣኑ ባደረገው ምልከታ አጣርቷል፡፡ በድርጊቱ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል ብዙዎቹ እንደተያዙም ባለስልጣኑ ሲገልጽ ተሰምቷል፡፡

ይህ አይነቱ ህገ ወጥ ድርጊት አሁን በደረስንበት የስልጣኔ ዘመን ፍጹም ሊደረግ አይገባውም፡፡ ማንኛውም ጥያቄ ወይም ቅሬታ የሚቀርብበት ህጋዊ ስርዓትና ምቹ ሁኔታ እያለ አድማ በመምታት ወይም በማኩረፍ ጥያቄ እንዲመለስ ጫና ማሳደር አግባብ አይደለም፡፡ በባለስልጣኑ በተዘረጋው የቅሬታ መፍቻ ስርዓት በጣም የተጋነነ፣ ነባራዊ የንግድ እንቅስቃሴውንም የማይገልጽ ግምት ቀርቦ የባለስልጣኑ ቁጥጥር ኮሚቴ ማስተካከያ ካላደረገበት ይህንኑ ቅሬታውን በህገ መንግስቱ መሰረት ገለልተኛ ሆኖ በተቋቋመው ነጻ የዳኝነት አካል ድረስ አቅርቦ መከራከር ይቻላል፡፡

በህገ መንግስቱ አንቀጽ 79 ንዑስ አንቀጽ ሁለት በተቀመጠው መሰረት በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የዳኝነት አካል ከማንኛውም የመንግስት አካል፣ ከማንኛውም ባለስልጣን ሆነ ከማንኛውም ሌላ ተጽእኖ ነጻ በመሆኑ ኮሚቴው ባግባቡ ያልተመለከተው ነገር ካለ እንኳን ፍርድ ቤቱ ሊመለከተው የሚችልበት ስርዓት አለ፡፡  

ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን ከዘጉ ሸማቹ ይጎዳል፣ የተረጋጋ የንግድ ስርዓት እንዳይሰፍንም ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ በአገር ኢኮኖሚ ላይም ኪሳራ ሊያስከትል ይችላል፡፡ በመሆኑም ሰሞኑን በአንዳንድ አካባቢዎች የታየውን አይነት ሱቅ የመዝጋት ሁኔታ ለነጋዴውም፣ ለሸማቹም ለሀገርም አይጠቅምምና በእንዲህ ዓይነት ህገወጥ ተግባራት ላይ አውቆም ይሁን ግራ ተጋብተው የተሳተፉ አካላት ይህ ጉዳይ ቆም ብለው ሊያስቡት ይገባል፡፡ የባለስልጣኑ ህዝብ ግንኙነት ክፍልም እንዲህ ዓይነት ነገሮችን አስቀድሞ በመገንዘብ ችግሮች ሳይከሰቱ በፊት ለመከላከል ካልሰራ የኮሙኒኬሽን ስራው ውጤታማነት የቱ ጋር ነው የሚል ጥያቄን ያጭራል።  ስለሆነም የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ነጋዴው ከባህላዊ አሰራር ወጥቶ ወደ ዘመናዊ አሰራር እንዲሻገር የማስተማርና ግንዛቤ የመፍጠር ሰፊ ስራውን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይስራበት ለማለት እንወዳለን፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

በቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ ላይ ጥናት ለሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን ወጣት ተመራማሪዎች ትኩረት እንደሚሰጥ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ 

ስድስተኛው የምሥራቅ አፍሪካ የቅድመ ሰው ዘር ጥናት ማህበር ትናንት በአዲስ አበባ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ለሶስት ቀናት የሚቆይ ኮንፍረንስ በተጀመረበት ወቅት ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም፤ ለኢትዮጵያውያን ወጣት ተመራማሪዎች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መንግሥት አስፈላጊ ነገሮችን እያሟላ ይገኛል ብለዋል፡፡ በባለስልጣኑ የነበረውን ቤተ ሙከራ ዘመናዊ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም አዳዲስ ወጣት ተመራማሪዎችን ወደ ዘርፉ ለማስገባት እንዲቻል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቅድመ ሰው ዘር ጥናት ትምህርት ክፍሎች ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዶክተር ሂሩት ገለጻ፤ በዘርፉ ሊያስተምሩ የሚችሉ የዶክትሬት ዲግሪ የትምህርት ዝግጅት  ያላቸው እንዲሁም፤ ውጪ አገራት ተልከው ሥልጠና እየወሰዱ የሚገኙ ተመራማሪዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፤ ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድጋፎች እየተደረጉ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት፡፡ 

በተለያዩ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ሲካሄድ የቆየው የቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ማህበር የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ነው፡፡ ጥናቱ ከሐምሌ 24 እስከ ሐምሌ 26 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ ይካሄዳል፡፡ ከተለያዩ አገራትና ከአገር ውስጥ ባሉ ተመራማሪዎች ስለቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ በርካታ የጥናት ወረቀቶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡

ዋለልኝ አየለ 

 

Published in የሀገር ውስጥ

የአዲስ አበባ ከተማ ለመንገድ ዳር መብራቶች  ትኩረት በመስጠት በአዲስ መልክ በሰፊው ለመስራት እቅድ እንዳለው የአዲስ አባባ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

   በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የራስ ኃይል አስፋልት መንገድ ጥገና ስራዎች ዳይሬክተር ኢንጂነር መኮንን ጥበቡ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት በከተማዋ አብዛኞቹ የመንገድ ዳር መብራቶች በብልሽት የቆሙና የማይሰሩ በመሆናቸው በአዲሱ በጀት ዓመት የተለየ ትኩረት በመስጠት ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተያዘ ልዩ በጀት ይሰራል፡፡

   እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በአዲስ መልክ የሚሰሩት የመንገድ ዳር መብራቶች ለእግረኛም ለትራፊክም የሚያገለግሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የሚተከሉት የመብራት ዓይነት ወደፊት ተለይተው የሚታወቁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ መብራቶቹ ከአሁን ቀደም ከነበሩት በተሻለ መልኩ ስለሚሰሩም የነበረውን ችግር ይፈታሉ ተብሎ ታምኖባቸዋል፡፡ ስራውንም በራስ ኃይል የመንገድ ጥገና ስራዎች ዳይሬክቶሬት ሙሉ በሙሉ እንደሚያከናውን ገልፀዋል፡፡

   የአዲስ አባባ መንገዶች ባለስልጣን በሁሉን አቀፍ የመንገድ ጥገና በተለይም አስፋልት ጥገና በበጀት አመቱ ካስቀመጠው  እቅድ በላይ ማከናወኑ የሚታወስ ነው፡፡ 

አስናቀ ፀጋዬ

Published in የሀገር ውስጥ

  የሙገር ኮሚዩኒቲ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት አዳራሽ በሰዎች ተሞልቷል፡፡ ተጋባዥ እንግዶችም ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ በጋራ ያገናኛቸው በሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ የቀድሞ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ግዛው ተክለማሪያም አማካኝነት በተመሰረተው የአትሌት ገዛኸኝ የመጀመሪያ ደረጃ  ትምህርት ቤትና የሙገር 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ከምስረታው ጀምሮ የተማሩ የመጀመሪያ ዙር ተማሪዎችን በጋራ ለማስመረቅ ነበር፡፡ ተማሪዎቹ በነዚህ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ  በዘንድሮው ዓመት ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች  በዲግሪ  የተመረቁ ናቸው፡፡ የምርቃት ስነ ስርአታቸውም በቤተሰቦቻቸው አዘጋጅነት ከትናንት በስቲያ በሙገር ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡

    ተማሪ ጌታቸው ፈይሳ ከአንደኛ ደረጃ እስከ መሰናዶ ድረስ ትምህርቱን የተከታተለው በሙገር ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ በዘንድሮው አመት ተመርቋል፡፡ የምርቃት ስነስርአቱ በጋራ መሆኑ በተለይም ከታች ለሚማሩ ተማሪዎች ከፍተኛ የሞራል ስንቅ እንደሚሆናቸውና ትልቅ መነሳሳት እንደሚፈጥር ያስረዳል፡፡ የምርቃት ስነስርአቱን በጋራ ለማካሄድ ቤተሰቦቻችን ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ የሚለው ተማሪ ጌታቸው ለእነርሱ ያለውን ምስጋናም ገልጧል፡፡ እንዲህ አይነቱ የምረቃ ስነ ስርአት በተበታተነና በግለሰብ ደረጃ ከሚሆን በጋራ መሆኑ ወጪና ጊዜን ከመቆጠብ ባሻገር የዘመናዊነት መገለጫ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ከዚህ በኋላ ለሚመረቁ ተማሪዎችም ተመሳሳይ  የምርቃት ስነስርአት ቢካሄድ የተሻለ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

     ወይዘሮ እመቤት አለሙ ልጃቸውን ካስመረቁ ወላጆች መካከል አንዷ ናቸው፡፡ ተማሪዎችን በጋራ የማስመረቁን ሃሳብ የጠነሰሱት እሳቸው መሆኑን ገልፀው፤ ከዚህ በፊት በአካባቢው በየአመቱ ተማሪዎች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲመረቁ የምርቃት ፕሮግራም በግለሰብ ደረጃ በየቤቱ ይካሄድ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ ይህም ወላጆችን ለአላስፈላጊ ወጪ የሚዳርግና ከቦታ አንፃርም በቂ ባለመሆኑ ተማሪዎቹን በአንድ ቦታ በተመሳሳይ ጊዜ ማስመረቅ እንዳስፈለገ ይጠቅሳሉ፡፡ ቀደም ሲልም ህብረተሰቡ በችግርም ሆነ በሃዘን አብሮ የማሳለፉ ባህል ነበረው፤አሁን ደግሞ ተማሪዎችን በጋራ የማስመረቁ ባህል በተለይም ማህበራዊ ትስስርንና አብሮነትን ለመጨመር እንደሚረዳም ነው የሚገልፁት፡፡

    የሙገር ኮሚዩኒቲ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አቶ ደሳለኝ ገመቹ እንደሚገልፁት  የተማሪዎቹን የምረቃ ስነስርዓት በጋራ ለማካሄድ ያነሳሳቸው ዋነኛ አላማ  በዘንድሮው አመት ከዩኒቨርስቲዎች የተመረቁ ተማሪዎች ከአፀደ ህፃናት  እስከ መሰናዶ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን በዚሁ በሙገር ኮሚዩኒቲና በገዛኸኝ አበራ ትምህርት ቤት በመማራቸው እንዲሁም የሙገር ሲሚንቶ ህብረተሰቡን በትምህርት ምን ያህል እያገዘ መሆኑን ለማሳየት መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር የትምህርት ቤቶቹን መስራች የቀድሞው የሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ግዛው ተክለማሪያምን ምስጋና ለመቸርም ጭምር እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

    እንደ አቶ ደሳለኝ ገለፃ ተማሪዎችን በጋራ ማስመረቁ ዋነኛ ጥቅሙ በትምህርት ላይ ያሉ ተማሪዎች የእነርሱን አርአያ እንዲከተሉና ትልቅ መነሳሳት በውስጣቸው እንዲኖር ያስችላል፡፡ ከዚህም ባሻገር ቤተሰብም በተመሳሳይ ልጁን ለማስመረቅ እርስ በእርስ እንዲፎካከርና በመሃከላቸው መንፈሳዊ ቅናት እንዲኖር እድል ይሰጣል፡፡

     የትምህርት ቤቱ መስራችና የቀድሞው የሙገር ሲሚንቶ ኢንትርፕራይዝ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ግዛው ተክለማሪያም በበኩላቸው  የአካባቢው ህዝብ  እስካለ ድረስ ሙገር አብሮ እንደሚቀጥል ገልጸው በተለይም ፋብሪካው የአካባቢውን ህብረተሰብ በማሳተፍ በጋራ መስራት መቻሉ የውጤታማነቱ አንዱ ሚስጥር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎችንና የሙገር ማህበረሰቦችን ለመጥቀም ትምህርት ቤት ማቋቋማቸውን ገልፀው፤ የተማሪዎቹ የጋራ ምርቃትም  ሙገር በትምህርት ረገድ ህብረተሰቡ ጋር መድረሱን የሚያሳይ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች የአካባቢውን ህብረተሰብ መልሰው ማገልገልና ማበረታታት እንዳለባቸውም ያሳስባሉ፡፡ ቤተሰቦችም ቢሆኑ ልጆቻቸው ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርሱ ማበረታታት እንዳለባቸው ይገልፃሉ፡፡

ዜና ሃተታ

አስናቀ ፀጋዬ

Published in የሀገር ውስጥ

ኢትዮጵያ ከቻይና አጋር አገራት መካከል በግንኙነት የላቀ ደረጃ ያላት አገር መሆኗን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር የነበሩት ሚስተር ላ ይፋን ገለጹ፡፡

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩትንና የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር  ሚስተር ላ ይፋን ትናንት ሸኝተዋቸዋል፡፡

  አምባሳደር ላ ይፋን እንደተናገሩት፤ የሁለቱም አገራት ግንኙነት እየጠነከረ መምጣቱን እና ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።

ባለፈው ግንቦት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቻይና ባደረጉት ጉብኝት ሁለቱም አገራት ግንኙነታቸው ሁሉን አቀፍ፣ ስትራቴጂካዊ እንዲሁም ትብብር ላይ የተመረኮዘ ለማድረግ መስማማታቸውን አስታውሰው፤ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከአገራቸው አጋር አገራት የላቀ የግንኙነት ደረጃ ያላት አገር መሆኗን የሚያሳይ መሆኑን አምባሳደሩ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆን በዓለም አቀፍ ሰላምና መረጋጋት መጠበቅ የራሷን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደምትገኝ በመጠቆም፤ ይህም አገሪቷ በዓለም አቀፍ መድረኮች የምትጫወተው ሚና እያደገ መምጣቱን  የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቻይና የኢትዮጵያ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ የፋይናንስ ምንጭ መሆኗን፣ በርካታ የቻይና ባለሃብቶችና ባለሙያዎች በኢትዮጵያ የልማት ሥራዎች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙና ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በቻይና የሚያገኙት የትምህርት ዕድል እያደገ መምጣቱ ግንኙነቱ የላቀ እንዲሆን ማድረጉን ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል፡፡ ተሰናባቹ አምባሳደር በቆይታቸው፤ የሁለቱን አገራት ግንኙነት የሚያጠናክሩ ተጠቃሽ ሥራዎች ማከናወናቸውንም ለተሰናባቹ አምባሳደር ገልጸውላቸዋል፡፡

በሪሁ ብርሃነ

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።